የቻድ መንግሥት የቦኮሐራም ታጣቂዎችን ለመደምሰስ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን ገለጸ
👉እሁድ ዕለት በቻድ ወታደራዊ ካምፕ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 40 ያህል ሰዎች ተገድለዋል
ጥቅምት 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመካከለኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ቻድ ሐይቅ አካባቢ በሚገኝ የጦር ካምፕ ላይ በሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት 40 የሚጠጉ ወታደሮች መገደላቸው ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም የቻድ ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቦኮ ሐራም ታጣቂዎችን ለመደምሰስ ወታደራዊ ዘመቻ ማስጀመራቸው የፕሬዚዳንቱ መግለጫ አስታውቋል።
ቦኮ ሐራም ካሜሩን፣ ናይጄሪያ፣ ኒዠር እና ቻድን በሚያዋስነው በቻድ ሐይቅ አካባቢ ድንገተኛ ጥቃት አድርሶ ብዛት ያላቸው የቻድ ወታደሮችን መግደሉ ነው የተገለጸው።
ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ ከጥቃቱ በሗላ በሰጡት መግለጫ፤ የእሁዱን ጥቃት በቦኮ ሐራም መፈጸሙን ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት አካባቢውን የጎበኙት ፕሬዝዳንቱ የተገደሉትን ወታደሮች ሥርዓተ ቀብር በማስፈጸም ርዳታ ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን፤ ከቀብር ስነ ስርአቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር ጥቃቱን የፈፀሙትን የቦኮ ሐራም ታጣቂዎች ለመደምሰስ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን መግለፃቸውን አናዶሉ ዘግቧል።
ቦኮ ሐራም እ.ኤ.አ በ2009 በናይጄሪያ በከፈተው ዓመጽ ከ40 ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ቡድኑ ጥቃቱን ወደ ጎረቤት ሀገራት አዛምቷል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ:www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ:http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ፡ www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በሰብል ላይ ከባድ አደጋ ሊያደርስ የሚችል የግሪሳ ወፍ በ5 ወረዳዎች መከሰቱ ተገለጸ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን 5 ወረዳዎችና በኦሮሚያ ልዩ ዞን 2 ወረዳዎች ላይ የግሪሳ ወፍ መከሰቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ አስላከ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የግሪሳ ወፉን መከላከል ካለተቻለ ልክ እንደ አንበጣ ሰብሎችን በሰፊው የሚያጠቃ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ "ወደ ሌሎች ቦታዎችና ሰብሎች ላይ እንዳይዛመትና እንዳይስፋፋ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡
በዚህም ቢሮው ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር በአውሮፕላን በመታገዝ የኬሚካል እርጭት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
አውዳሚ የግሪሳ ወፉ የተከሰተባቸው ቦታዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ቀውት፣ ጊሌ ና ሽዋሮቢት ወረዳዎችና ወደ 8 ቀበሌዎች ላይ ነው ሲሉሜ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
አክለውም በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ወይም ከሚሴ አካባቢ ዳዋና ኤፍራታ ወረዳዎችና 5 ቀበሌዎች ላይ መከሰቱንም ዶክተር ማንደፍሮ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ግሪሳው ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዳይስፋፋ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአለምነው ሹሙ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራና በትግራይ ክልሎች ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉ አሳሳቢ ነው ተባለ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራና በትግራይ ክልሎች እስካሁን ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉ አሳሳቢ ነው ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ነገር በጦርነት ይፈታል የሚል እሳቤ ባለበት እንዴት ነው ሀገር የምትመክረው ሲሉም ፖለቲከኞቹ ተናግረዋል፡፡
ከአሐዱ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ኢህአፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ ተወካይ አቶ ኢሳቅ ወልዳይ "ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ገለልተኝነቱም ጥያቄ ውስጥ ወድቋል" ብለዋል፡፡
"የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁሉንም ያካተት አይደለም" የሚሉት አቶ ኢሳቅ፤ "ከዚህ በላይ ዋናው አሳሳቢ ጉዳይ ሁሉም ነገር በጦርነት ይፈታል ተብሎ እየታሰበ ሀገር እንዴት ነው የምትመከረው?" ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተለይም በአማራ እና ትግራይ እንዲሁም ኦሮሚያ የተወሰኑ ቦታዎች ጭምር ባለው ችግር ምክንያት ምክክር አለመጀመሩ ብቻም ሳይሆን "ገለልተኛ ኮሚሽን አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኢህአፓ ቀድሞውንም እራሱን ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዳገለለ የሚያነሱት አቶ ኢሳቅ፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የማስፈፅም አቅሙ ውስን መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በተጨማሪም በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሽግግር መንግሥትን ያስፈልጋል የሚሉ ሃሳቦችን ማንሳት እንደሀገር ጠላትነት ተደርጎ የቀረበበት መንገድ መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡
ሌላኛው በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት የአንድ ኢትዮጵያ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአማራና ትግራይ ክልሎች ምክክር ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይሁን እንጂ "ምክክር አድርገናል በተባለባቸው ክልሎች ላይም ዕምነት የለንም" ያሉ ሲሆን፤ ከአማራ እና ትግራይ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ እና ሶማሊያ ክልሎችም ቅሬታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ "ውይይት አድርጌባቸዋለው" ባላቸው ቦታዎችም ጭምር በትክክል ማንን እንዳነጋገረም ተዓማኒ የሆነ መረጃ እየሰጠ አይደለም ሲሉም ቅሬታቸውን በመግለጽ፤ "ኮሚሽኑ አስተያየትም ሲሰጠው የሚቀበል አይደለም" ብለዋል፡፡
በኮሚሽኑ ዕምነት እንዳጡ የሚያነሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ዘላቂ መፍትሄ ይመጣል ብለው እንደማያምኑም ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች "ፋይዳ" መታወቂያ መቅረብ ግዴታ ነው አለ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በአዲስ አበባ በሚገኙት 16 ቅርንጫፎች ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ደንበኞች "ፋይዳ" ዲጂታል መታወቂያ ማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው አስታወቀ።
በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎት ለማግኘት "ፋይዳ" ዲጂታል መታወቂያ ወይም የተመዘገቡበትን ማስረጃ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት አገልግሎቱ ባወጣው መረጃ ጠቁሟል።
በመሆኑም ከሕዳር 1 ቀን 2017 ጀምሮ ተቋሙ ለሚሰጠው አገልግሎት ደንበኞች ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ወይም የተመዘገቡበትን ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው አሳስቧል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ያለምንም ሕጋዊ ደረሰኝ 'የኮቴ' እንድንከፍል እየተገደድን ነው ሲሉ ገለጹ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከአዲስ አባባ ወደ አማራ ክልል ደቡብ ጎንደር እና ከአዲስ አባባ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዳንጎቴ መስመር የሚያሽከረክሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ያለምንም ሕጋዊ ደረሰኝ ለትራፊኮች 'የኮቴ' እየከፈልን ነው ሲሉ ለአሐዱ ቅሬታቸውን አቀርበዋል፡፡
በዚህም አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል ዳንጎቴ መስመር የሚያሽከረክሩ ቅሬታ አቅራቢ፤ በትራፊኮች ያለ አግባብ ጫና እየደረሰባቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በመስመሩ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችም ከዚህ ቀደም ታግተው እስከ 500 ሺሕ ብር የሚደርስ ክፍያ ከፍለው መለቀቃቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የከባድ መኪና አሽከርካሪ በበኩላቸው፤ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ጎንደር መስመር የከባድ ጭነት መኪና እንደሚያሽከረክሩ ገልጸው፤ በታጣቂዎች እንግልት እንደሚደርስባቸውና ሕጋዊ ባለሆነ መልኩ በትራፊኮች የኮቴ እየተጠየቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አሐዱ መነሻቸውን ከአዲስ አባባ ወደ የኦሮሚያ እና አማራ ክልል መስመሮች አድርገው ከባድ መኪና የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን ቅሬታ ተቀብሎ የሚመለከተውን የፊደራል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ቢሮ አነጋግሯል፡፡
የፌደራል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ የህዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አመለወረቅ ህዝቅኤል በሰጡት ምላሽ፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ክልሎቹ ቢሆንም ፤ ችግሩን ለመቅረፍ እንደፌደራል በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ እየተከናወነ ስላለው ሥራ ግን በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
ነገር ግን አሽከርካሪዎቹ ከሁለቱ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ ሲገቡም ሆነ ከአዲስ አባባ ሲወጡ የደህንነት ስጋት እያደረባቸው መሆኑን ገልጸው፤ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በደረጄ መንግስቱ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የአራተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬ ረፋድ እያከናወነ ውሏል
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ናቸው፡፡
በዛሬው የምክር ቤቱ ውሎ ላይም ይህን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን ምክር ቤቱ ካዳመጠ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
እንዲሁም ምክር ቤቱ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ በቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል፡፡
በውይይቱም አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ሀሳቦች እና አስተያየቶች ከምክር ቤት አባላት ሲሰጡ አርፍደዋል፡፡
የቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ዙሪያም ገንቢ ናቸው የተባሉ ሀሳቦችን ተሰንዝረዋል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሳባው የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት በአብላጫ ድምጽ በምክርቤቱ አጸድቋል፡፡
በዛሬው እለት ከቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሦስት አዋጆችን በምክርቤቱ ጸድቀዋል፡፡
የከተማ መሬት ይዞታን እና መሬት ነክ ምዝገባን ረቂቅ አዋጅ፤ ለከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙኃን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
በአማኑዔል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ምክር ቤቱ የ5 ሚኒስትሮችን ሹመት አጸደቀ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት እያካሄደው በሚገኘው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት በአብላጫ ድምጽ አጸድቋል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 72 ንዑስ 2 ላይ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊነት ቦታዎች ሹመት እንፀድቅላቸው በደብዳቤ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሹመቱ በምክር ቤቱ እንዲጸድቅ ቀርቧል።
ሹመታቸው እንዲጸድቅ በምክር ቤቱ የቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት የምክር ቤቱ አባላት የሚኒስትሮቹ ሹመት ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ ሹመቱን በአንድ ተቃውሞ፣ በሁለት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቀዋል። ተሿሚ ሚኒስትሮችም በምክር ቤቱ ተገኝተው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
በተጨማሪም የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ጸድቋል፡፡
እንዲሁም ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን ምክር ቤቱ ካዳመጠ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ብሔራዊ መታወቂያን ለሀገር ውስጥ በረራዎች በጉዞ ሰነድነት መጠቀም የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም (ፋይዳ ለኢትዮጵያ) ስርዓቶቻቸውን በማቀናጀት፤ ብሔራዊ መታወቂያን ለሀገር ውስጥ በረራዎች በጉዞ ሰነድነት መጠቀም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በስምምነቱም መሠረት፤ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመሆን ምዝገባ ከመያዝ ጀምሮ እስከ መሳፈር ድረስ ያለውን የመንገደኞች አገልግሎት "ባዮ ሜትሪክ" መረጃን በመጠቀም ይበልጥ ለማቀላጠፍ እንደሚሰራ አየር መንገዱ አስታውቋል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በድሬደዋ እና ሱማሌ ክልል ሲቲ ዞን መካከል በተከሰተ የሰደድ እሳት ምክንያት ለጊዜው የባቡር እንቅስቃሴ መቆሙ ተገለጸ
ጥቅምት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በድሬደዋ እና ሱማሌ ክልል ሲቲ ዞን መካከል አሁን በተከሰተው የሰደድ እሳት ምክንያት ለጊዜው የባቡር እንቅስቃሴ መቆሙን የኢትዮ- ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢ/ር ታከለ ኡማ አስታውቀዋል።
በዚህም እሳቱን ለመቆጣጠር እና አገልግሎቱን ለማስጀመር የድሬደዋ የእሳት አደጋ እና የሽንሌ ዞን ሀላፊዎች ከጣቢያው ሰራተኞች ጋር በመሆን ባደረጉት ርብርብ እሳቱን ማጥፋት መቻሉን ኢ/ር ታከለ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋልል።
ኢ/ር ታከለ አክለውም ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት ለተረባረቡት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
"ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዕዉቅና መስጠት ኃላፊነቴ አይደለም" ምርጫ ቦርድ
ጥቅምት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዕዉቅና መስጠት ኃላፊነቴ አይደለም ሲል ገልጿል፡፡
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዉብሸት አየለ፤ "የዕዉቅና ጉዳይን በተመለከተ በአዋጅ 1162/2011 ላይ በግልፅ እንደተመለከተዉ ቦርዱ የጋራ ምክር ቤት ማቋቋም እንደሚችል በተቀመጠዉ መሠረት አቋቁመነዋል" ብለዋል።
"ለመሆኑ ምርጫ ቦርድ የጋራ ምክር ቤቱን ካቋቋመዉ እንዲሁም ቢሮ ተከራይቶ የሚያስተዳድረው ከሆነ ለምን ዕዉቅና መስጠት አልቻለም?" ሲል አሐዱ ጠይቋል።
የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዉብሸት አየለም "ይህንን ማድረግ ቦርዱን አይመለከትም" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ2011 መጋቢት ላይ መቋቋሙን ያነሱት ምክትል ሰብሳቢዉ፤ ሲቋቋም ሁለት መሠረታዊ ሀሳቦችን በመያዝ ነዉ ብለዋል።
"ይህም በፖርቲዎች መካከል ያለመግባባት ሲኖር ያንን ለመፍታት ሲሆን፤ ሁለተኛዉ ደግሞ ፖርቲዎች ለአባላቶቻቸዉ ትምህርት የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነዉ" ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም ምክር ቤቱ እነዚህን የማስተባባር ሃላፊነት ወስዶ እየሰራ ነዉ ያሉት አቶ ዉብሸት፤ "በአዋጁ ላይም እንዴት መንቀሳቀስ እንደሚችል በግልፅ ተቀምጧል" ብለዋል።
"ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ አሁን ባለበት መንገድ የሚቀጥል እንጂ ፖርቲዎችን የማስተዳደር ሃላፊነት የተሰጠዉ ለምርጫ ቦርድ ብቻ ነዉ" ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ የዕዉቅና ይሰጠኝ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አለማግኘቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ምርጫ ቦርድም "እዉቅና መስጠቱ የእኔ ድርሻ አደለም" ብሏል።
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ምክንያት አለመከፈታቸው ተገለጸ
ጥቅምት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ምክንያት ባለመከፈታቸው ተማሪዎች እየተጎዱ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ደሳለኝ አያና ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው እንዳሉት በዞኑ ውስጥ ችግሮችን ተቋቁመው እየሠሩ ያሉት ከ238 ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ 101 ትምህርት ቤቶች ትምህርት አልጀመሩም፡፡
እስካሁን ድረስም 100 ሺሕ 656 ተማሪ መመዝገብ የነበረበት ሲሆን፤ በዞኑ ባጋጠመው የጸጥታ ሁኔታ ተማሪዎች ትምህርት ለመከታተል አለመቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ደሳለኝ አያና ገለጻ ከሆነ ሥራ በጀመሩ 100 ትምህርት ቤቶች 21 ሺሕ 673 ተመሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡
ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አኳያ በዞኑ 10 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ ሰባት ትምህርት ቤቶች ምዝገባ አካሂደው ወደ ትምህርት ገበታቸው ስለመመለሳቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
ኃላፊው ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት እና የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዳያከናውኑ እንቅፋት በመፍጠር ለመደራደሪያነት የሚጠቀመው ኃይልም ራሱን ቆም ብሎ ማየት እንደሚገባው ነው የተናገሩት፡፡
አቶ ደሳለኝ በዞኑ የሚገኙ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው ትምህርታቸውን ያለ እንከን መከታተል እንዲችሉ እንዲደረግ ሁሉም መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በዞኑ በኩል ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይነጠሉ ለማስቻል ከማኅበረሰቡ ጋር በተከታታይ ውይይት እየተካሄደ ስለመሆኑም ማብራራታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
በሚካሄዱ መድረኮች ኅብረተሰቡ ስለ ጉዳዩ ግልጽ እንዲሆን እና በባለቤትነት ወስዶ እንዲሠራ እየተሠራ ያለው ሥራ ለውጥ እያሳየ ስለመሆኑም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
አቶ ደሳለኝ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሁሉም አካል ትምህርት የአንድ ሀገር ምሰሶ በመሆኑ በዘርፉ ላይ ከሚደረግ ጫና ራሱን እንዲያቅብ ጠይቀዋል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ሱዳን የኢትዮጵያ 60 ሚሊየን ዶላር እዳ እንዳለባት ተገለጸ
ጥቅምት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሱዳን ከኢትዮጵያ ወስዳ የተጠቀመችበትን የኤሌክትሪክ ሽያጭ ዋጋ 20 ሚሊየን ዶላር ያህሉን መክፈሏ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ሽያጭን ከምታደርግባቸው አጎራባቾች መካከል አንዷ ሱዳን ስትሆን፤ አሁን ላይ ከ100 ሜጋ ዋት ወደ 10 ሜጋ ዋት ዝቅ ያለ የሐይል መጠን እየተጠቀመች መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታውቋል፡፡
ከዚህ በፊት ከነበረባት 80 ሚሊየን ዶላር እዳ ውስጥ አሁን ላይ ወደ 60 ሚሊየን ዶላር መውረዱ ተመላክቷል፡፡
ቀሪውን እዳ የምትከፍልበት ጊዜ ገደብ ባይቀመጥም በየጊዜው እዳዋን እየቀነሰች ትሄዳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ያለው የመግባቢያ ሰነድ ሱዳን እዳዋን ባትከፍል እስከ ዓለማቀፍ ፍርድ ቤት መሄድ የሚያስችል እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታቀርብ ሲሆን፤ አሁን ላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል።
በተመሳሳይ በቀጣይ ለታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በመጀመሪያው የ2017 ሩብ ዓመት ማለትም ባለፉት ሦስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ብቻ ከቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ፤ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በእመቤት ሲሳይ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ምርመራ አሁንም በሂደት ላይ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ
ጥቅምት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ በትውልድ ከተማቸው መቂ ከተማ ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም መገደላቸው ይታወቃል።
አሐዱም ግድያውን ተከትሎ ምርመራ የጀመረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን "ምርመራው ከምን ደረሰ?" ሲል ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መሰለ ለአሐዱ በሰጡት ምላሽ፤ "የፖለቲከኛ በቴ ኢርጌሳን ግድያ በተመለከተ የተጀመረው ምርመራ በሂደት ላይ ነው" ሲሉ ገለጸዋል።
አክለውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምርመራው ሂደት የቀጠለ ሲሆን፤ "ምርመራዉ ላይ ባለ ጉዳይ ይህ ነው ማለት አይቻልም" ብለዋል፡፡
ከምርመራው በኃላ ቢሆን ውጤቱ ይፋ የሚደረግበት አሊያም የማይደረግበት ሁኔታ መኖሩን ተጠባባቂ ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
አቶ በቴ የካቲት አጋማሽ ላይ በቁጥጥር ሥር ውለው ለሁለት ሳምንታት ያህል በእስር ከቆዩ በኋላ በ100 ሺሕ ብር የገንዘብ ዋስትና የተለቀቁት የካቲት 30/2016 ዓ.ም ነበር።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ግድያውን ተከትሎ አደረኩት ባለው ማጣራት "ግድያቸው ፖለቲካዊ ነው" ሲል መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም።
በተመሳሳይም ኢሰመኮ የፖለቲከኛው ግድያ ላይ የሚያደርገውን ምርመራ እንዲቋርጥ "ጫና እየተደረገብኝ ነው" ማለቱም ይታወሳል።
በፍርቱና ወልደአብ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡ https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፡ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ፡ www.tiktok.com/@ahadutv.official
"ሀሰተኛ የሴት አባላት ቁጥር ሪፖርት ያቀረቡትን ፓርቲዎች ነው ያገድኩት" ምርጫ ቦርድ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ሴቶች በበቂ ሁኔታ ተገቢውን ስፍራ እያገኙ ባለመሆኑና ሀሰተኛ የሴት አባላት ሪፖረቶች በማቅረባቸው በአዋጁ መሰረት ያለተንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
"በአዋጁ መሰረት ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፎ ቁጥራቸውን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችንም በአባላትና አመራር ደረጃ ለማሳደግ ከገንዘብ ድጋፍ ጋር እንዲያያዝ አድርገነዋል" ሲሉ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን ማበረታቻ ገንዘብ ያላግባብ ለመጠቀም በማሰብ የተንቀሳቀሱት ፓርቲዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ሥራ መሰራቱን ምክትል ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡
"የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በ2014 ዓ.ም አንድ መቶ ሴቶች አሉኝ ያለ ሲሆን፤ በ2015 ግን ምንም ሪፖርት ባለማቅረቡ ምንም ድጋፍ አልተደረገለትም" ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ፓርቲው በ2016 ዓ.ም ተመልሶ ሪፖርት ሲያቀርብ በ2014 ዓ.ም የነበረው 100 ሴቶች በዕጥፍ አድጎ 72 ሺሕ ሴቶች በስሩ እንዳሉ አድርጎ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡
አቶ ውብሸት ሲቀጥሉም "በተደጋጋሚ ግዜ ፓርቲው በዚህ ዙሪያ ሲጠየቅ፤ 'ዜሮው በስህተት ነው የገባው' የሚል ተቀባይነት የሌለው ምላሽ ሰጥቶናል" ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የአገው ብሄራዊ ንቅናቄም በተደጋጋሚ የሚያቀርባቸው የሴት አባላት ቁጥር አጠራጣሪ በመሆኑ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ሊያቀርብ ባለመቻሉ ውሳኔ እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡
ሌሎች ሦስት ፓርቲዎች ስብሰባዎቻቸውን በልመና የሚተዳደሩ ሁሉ ሳይቀር በማሳተፍ በማቅረባቸው፤ እንደ ኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ያሉት መታገዳቸንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ምክትል ሰብሳቢው "ፓርቲዎቹ በተደጋጋሚ ገንዘቡን እንዲመለሱ ሲጠየቁም 'መረጃ የመያዝ ልምድ የለንም' እንዲሁም 'ልንጠየቅ አይገባም' የሚሉ ሀሳቦችን በማቅረባቸው ጭምር ነው የታገዱት" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ያገዳቸው ወደ 11 የሚጠጉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከማናቸውም ሕጋዊ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#አሐዱ_ትንታኔ
እስራኤልና ኢራን ወደለየለት ጦርነት የሚገቡ ከሆነ የአለም ኢኮኖሚ ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ኢራን ክእስራኤል የሚሰነዘሩባትን ጥቃቶች አጋናም አናንቃም እንደማትመለከታቸው ገልፃለች፡፡ የዛሬው የአለማቀፍ ትንታኔ ትኩረታችን ነው፡፡
ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/NtHwIiLB6uY?si=wqrpyRuhXEtMrikG
በድሬደዋ በሦስት ወራት ውስጥ በደረሱ ከ85 በላይ የትራፊክ አደጋዎች የ13 ዜጎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በድሬደዋ ከተማ በደረሱ ከ85 በላይ የትራፊክ አደጋዎች የ13 ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ መቻሉን የከተማዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት አስታውቋል፡፡
ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በደረሱ ትራፊክ አደጋዎች የሚሞቱ የዜጎች ቁጥር መጨመሩን የተናገሩት፤ በዳይሬክቶሬቱ የግንዛቤ ማስጨበጥና ማስፋፋት ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር ጌትነት ዳባ ናቸው፡፡
በአራት ዓመታት ውስጥ በመንገድ ደህንነት ላይ በተሰሩ ሥራዎች አማካኝነት የትራፊክ አደጋን መቀነስ መቻሉን የገለጹት ኃላፊው፤ ነገር ግን በሦስት ወራት ውስጥ በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
ለዜጎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሆኑ የትራፊክ አደጋዎች የደረሱት በድሬደዋ ከተማ በ01 እና በ02 ቀበሌ መልካ አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማው ደንገጎ ተብሎ በሚጠራው መስመር ከዝናብ እና በምሽት ከማሽከርከር ጋር በተያያዘ የትራፊክ አደጋ እንደደረሰም ተናግረዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም በስድስት ወራት ውስጥ ከ130 በላይ የትራፊክ አደጋ እንደደረሰ እና የሞት አደጋ 10 እንደነበር ኃላፊው ጨምረው አስታወሰዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የዛሬ ፕሮግራም ጥቆማ!
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚያዘጋጀውና የሰላም ግንባታ ላይ የሚያተኩረው ልዩ ፕሮግራም ዘወትር ማክሰኞ ከምሽቱ 11፤ 30 ጀምሮ በአሐዱ 94.3 ላይ ወደ እናንተ ውድ ቤተሰቦቻችን ያደርሳል፡፡
ፕሮግራሙን እንድትከታተሉና ሃሳብ እንድታደርሱን በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ፣ ይደውሉልን፡፡
በአዲሱ ስርአተ ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን የሚመለከተው አንቀጽ ተቃውሞ ገጠመው
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዛሬው ዕለት የተካሄደው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር-ቤት ጉባኤ የተለያዩ አዳዲስ ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር ዕያታ ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች ልኳል።
ከቀረቡለት አዋጆች መካከል የትምህርት ስርአቱን የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነው። በዚህ አዋጅ የአፍ መፍቻ ቋንቋን የተመለከተው ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል።
የአፍ መፍቻ ቋንቋን በትምህርት ስርአቱ ውስጥ መገልገል ስለሚቻልበት ሁኔታ የሚያብራራው የረቂቅ አዋጁ፤ ከዚህ በፊትም ጥያቄ፣ አስተያየት እና ተቃውሞ ሲያስተናግድ እንደቆየ ይታወሳል፡፡
የመንግስት ተጠሪ ሚንስትር ተስፋዬ በልጅጌ በንባብ ያቀረቡት አዲሱ የትምህርት ስርዓት ረቂቅ አዋጅ በርከት ያሉ ሃሰቦች እና አስተያየቶች ተሰንዝሮበታል።
በተለይም በትምህርት ስርዓቱ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ረገድ ረቂቅ አዋጁ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በትኩረት እንዲመለከተው የምክር ቤት አባላቱ አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ የምክር ቤት አባላቱ ያነሷቸውን ጥያቄዎች አዳምጦ የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ በማጽደቅ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡
በአማኑዔል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በጌድዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) ሹመት ላይ ከፍተኛ ወቀሳ ቀረበ
👉 "የተሰነዘረው አስተያየት ጥቅል ፍረጃ ያለበትና ተገቢው ምርመራ ያልተከናወነበት ነው" ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት እያካሄደው በሚገኘው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ፤ የም/ቤቱ አባልና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በቀድሞ የፍትህ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞትዬስ (ዶ/ር) ላይ ከፍተኛ ወቀሳ ሰንዝረዋል።
የምክር ቤት አባሉ በሹመቱ ላይ ባቀረቡት ቅሬታ፤ "የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብታችን ሳይነሳ እንደ ሽፍታ ተጎትተን ስንታሰርና ለወራት ስንቀመጥ ምን ሰሩ? " ሲሉ ጠይቀዋል።
አክለውም፤ "ሌሎች የምክር ቤት አባላት የፌዴሬሽን ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገቢ ፍትህ ሳያገኙ ለአመታት ሲንገላቱ የፍትህ ሚኒስትር ምንም የሰራው ነገር የለም። ከሳሹ እራሱ የፍትህ ሚኒስትር ነው።" ብለዋል።
ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ወደ ፍትህ ሚኒስቴር ሲመጡ ከፍተኛ ተስፋ አድርገው እንደነበር የገለጹት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፤ ነገር ግን ከሳቸው በፊት ከነበሩት ሚኒስትሮች ምን የተለየ ነገር አለማሳካታቸውን ለምክር ቤቱን ገልጸዋል።
"በሕግ ከውጭ ዩኒቨርሲቲ ፒኤችዲ ይዘው መምጣታቸውና እዚህም ትልቁ የሀገራችን ተቋም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማራቸው ላይ ምን ለውጥ አመጡ የሚለው አልተገመገመም" ብለዋል።
"እኔ በግሌ ቅሬታ አለኝ" ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር) " በፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን የእውቀት ችግር አለባቸው ብዬ አይደለም፤ በተለያዩ መድረኮች አይቻቸዋለሁ ሙያቸውን በጣም ጠንቅቀው ያውቃሉ ፤ ነገር ግን አፈጻጸማቸውን ካየነው የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረውን የፍትህ ጥማት ከማስታገስና ያን ከማርካት ይልቅ አሁንም የፍትህ ስርዓቱ የፖለቲካ መሳሪያ እንዲሆን አድርገዋል" የሚል ወቀሳም ሰንዝረዋል።
"በሀገራችን በተለይ በኢህአዴግ ዘመን የፍትህ ስርዓቱ ተቃዋሚዎችን ማጥቂያ፣ የፖለቲካ መሳሪያ፣ የገዢው ፓርቲ አንድ አርም ተደርጎ ሲሰራ ነበር አሁንም ያ ተቀይሯል ብዬ አላስብም" ብለዋል።
"ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲፈልገው የነበረውን የፍትሕ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የፍትሕ ሥርዓቱን ለፖለቲካ መጠቀሚያ አድርገውታል" ሲሉም ተናግረዋል።
"በዚህ ሂደት ውስጥ እንዴት አዲስ የካቢኔ ሹመት ማግኘት አለባቸው የሚለው ሂደትም ተገቢ ግምገማ ሳይከናወንበት የተደረገ ነው የሚል እምነት አለኝ" ሲሉም ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
በመሆኑም፤ "የፍትህ ዘርፉን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱ ስለሆኑ ትራክ ሪከርዳቸው የውጭ ጉዳይን ለመምራት ብቁ ሊያደርጋቸው አይገባም" ብለዋል።
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) አክለውም የሚኒስትሮች ሹመት ሂደት ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፤ "የሚነሱ ሚኒስትሮች ከሾምናቸው በኃላ ምን አጉለው እንደተነሱ፣ ምን ድክመት እንዳሳዩ፣ ወይ ምን የስነምግባር ጥሰት እንዳሳዩ አይቀርብም፣ በተጨማሪም እነሱን የሚታኳቸው ሚኒስትሮች ከነሱ በምን እንደሚሻሉ አይነገረም " ሲሉ ተናግረዋል።
"ይህም ከግልጽነት እና ከተጠያቂነት መርህ አንጻር ጥያቄ እየሚያስነሳ ነው" ሲሉ አሳስበዋል።
የመንግሥት ተጠሪ ሚንስትር የሆኑት ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ "የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በተሸሙት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ላይ የተሰነዘረው አስተያየት ጥቅል ፍረጃ ያለበትና ተገቢው ምርመራ ያልተከናወነበት ነው" ሲሉ ለቀረበው ወቀሳ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አክለውም "ተሿሚን ብቁ አይደሉም በሚል የተሰጠው ጥቅል ፍረጃም ነባራዊውን ሁኔታ ያገናዘበ ነው ለማለት ይከብደኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት እየተካሔደ በሚገኘው የምክርቤቱ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሹመት በቀረቡት አምስት ሚኒስትሮች ሹመት ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ሹመቱም በአንድ ተቃውሞ፣ በሁለት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ብቁ እና ንቁ ያልነበሩ የ1997 የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎች በተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች እየተስተናገዱ እንደሚገኝ ተገለጸ
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) "የ1997 የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎች ከየትኛውም የቤት ልማት መርሃ ግብር ውጪ እንደተደረጉ ተደርጎ የተሰራጨው መረጃ የሀሰት ነው" ሲል የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ገልጿል።
ቢሮው "ከአውድ ውጪ ተተረጎመ" ባለው መረጃ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በማብራሪያውም፤ "የ1997 የጋራ መኖርያ ቤት ተመዝጋቢዎችን በተመለከተ ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው የተሳሳተ መረጃ ትክክል ባልሆነ መልኩ ከአውድ ውጪ ተተርጉሞ የቀረበ ነው" ሲል ገልጿል።
አክሎም፤ ከተማ አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶች ለማስተላለፍ ባወጣው መመሪያ ቁጥር 3/2011 መሰረት ብቁ እና ንቁ ማለትም፤ "የቤት ፈላጊዎች በገቡት ግዴታ መሰረት የቁጠባ መጠን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትክክል ተቀማጭ ማድረጋቸውን ከእጣ በፊት ያረጋግጣል ይላል" ብሏል።
በዚህም መሠረት የ1997 ተመዝጋቢዎች በወቅቱ በመረጃ ቋት ውስጥ ንቁ እና ብቁ የነበሩ ተመዝጋቢዎችን ከተማ አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ አስተናግዶ ማጠናቀቁን የገለጸው ቢሮው፤ ነገር ግን በወቅቱ ብቁ ያልነበሩትን የ1997 ተመዝጋቢዎች እና ሌሎች የ2005 እጣ ያልደረሳቸው የቤት ፈላጊዎች እየተተገበሩ ባሉ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች እያስተናገደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ይህንን ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩትን ከተማ አስተዳደሩ በሕግ የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጿል።
አክሎም ከተማ አስተዳደሩ ተመዝግበው የሚጠባበቁትንም ሆነ ሌሎች የከተማችዋን የቤት ፈላጊዎች ቤት ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ አዳዲስ የቤት ልማት አማራጮችን በመቀየስ እየተገበረ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የ1997 የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎች ለረጅም ዓመታት የጋራ መኖሪያ (ኮንዶሚኒየም) ቤት ለማግኝት ተመዝግበውና ገንዝብ በባንክ ሲቆጥቡ ቆይተው እስካሁን የቤት ዕጣ ስላልወጣላቸው ቅሬታቸውን በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
የከተማ አስተዳድሩ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በቅርቡ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር በነበረ ውይይት ባደረጉት ንግግር፤ ከዚህ በፊት በ2015 ዓ.ም. በተላለፉት ቤቶች የ1997 ዓ.ም. ቆጣቢዎች ሁሉም ዕጣ እንዲወጣላቸው መደረጉንና ለተመዘገቡት ሁሉ ቤት ተሰጥቶ መጠናቀቁን መግለጻቸውም አይዘነጋም፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮም ባወጣው መረጃ በወቅቱ በመረጃ ቋት ውስጥ ንቁ እና ብቁ ለነበሩ የ1997 ተመዝጋቢዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ሰጥቶ መጨረሱን ገልጾ፤ ነገር ግን በወቅቱ እጣ ያልደረሳቸው የቤት ፈላጊዎች እየተተገበሩ ባሉ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች እየተስተናገዱ ይገኛሉ ብሏል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ያካሂዳል
ጥቅምት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ያካሄዳል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው፣ የምክር ቤቱን 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ መርምሮ የሚያጽደቅ ሲሆን፤ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታየ አፅቀስላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበን የድጋፍ ሞሽን ማዳመጥ እና የሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም የከተማ መሬትን በሊዝ ለመያዝ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን፣ የከተማ መሬት ይዞታ እና መሬት ነክ ንብረት ለመመዝገብ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ተገልጿል።
እንዲሁም ምክር ቤቱ፣ የመገናኛ ብዙሃን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከምክር ቤቱ የተገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#አሐዱ_ስንክሳር
ጥንቅሩን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/hUwrXQnQyPA?si=UY6nija0s8AJjyII
#አሐዱ_አንቀፅ
ጥንቅሩን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/7mPyTgO5OTw?si=NYdkLtTDN81mCrhk
"በዘፈቀደ ህጋዊ ያልሆነ ሹመት መስጠትና መንሳት የበጀት ቅጣትና የህግ ተጠያቂነት ያስከትላል" የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር
👉የመቀሌ ከተማ ም/ቤት "የተሾሙት ሹማምንቶች ሥራቸውን እንዳይሰሩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የፃፉትን ደብዳቤ ያንሱ" ሲል አሳስቧል
ጥቅምት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) "የጊዚያዊ አስተዳደሩ እቅዶች ማደናቀፍ እና በዘፈቀደ ህጋዊ ያልሆነ ሹመት መስጠትና መንሳት የበጀት ቅጣትና የህግ ተጠያቂነት ያስከትላል" ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አሳስቧል።
የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር በፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፊርማ ተፈርሞ በተሰራጨው መመሪያ ፤"በህወሓት አመራሮች የተፈጠረ የፓለቲካ ልዩነት ምክንያት በማድረግ መንግሥታዊ ስልጣን እና ሃላፊነት የሌለው 'ቡድን' የሚሰጠው ሹመት የመሻርና ሹመት የመስጠት ተግባር ፍፁም ተቀባይነት የለውም" ብሏል።
በመሆኑም ፦
1. ቡድኑ የሚያካሄዳቸውን ሕጋዊ ያልሆኑ ተግባራት እንዲቆም ፤ ይህንን የጊዚያዊ መንግሥቱ መመሪያ በመቀበል ፍርድ ቤት ጨምሮ የዞን እና የወረዳ የመንግስት መዋቅሮች ህጋዊ አሰራር እንዲከተሉና ህግ በሚጥስ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ፤
2. በክልሉ በየመዋቅሩ ያሉ ምክር ቤቶች ጊዚያቸው ያለፈ እና ህጋዊ መሰረታቸው ያበቃ መሆኑን በመቀበል ሹመት ከመስጠትና ከመሻር እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቅያ ሰጥቷል።
ከዚህ ባለፈ የጊዚያዊ አስተዳደሩን እቅዶች የሚፃረር የከተማና የገጠር ወረዳ የአስተዳደር መዋቅር በጀት እስከመገደብ የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልበት በአፅንኦት አሳስቧል።
በሌላ በኩል የመቀሌ ከተማ ምክር ቤት አስተባባሪ ኮሚቴ "የተሾሙት ሹማምንቶች ሥራቸውን እንዳይሰሩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የፃፉትን ደብዳቤ እንዲያነሱት" የሚያሳስብ መግለጫ አውጥቷል።
ኮሚቴው የወረዳ፣ ከተማ፣ ክፍለ ከተማ እና የጣብያ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን በትግራይ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 77/4/ መሰረት አምስት ዓመት መሆኑን በመግለጽ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የመቀሌ ከተማ ከንቲባውን ህግና ስርዓት ባልተከተለ መልኩ ሥራቸውን እንዳይሰሩ የእግድ ደብዳቤ የጻፉ መሆኑን በማንሳት አስተዳደሩ ባስቸኳይ ደብዳቤው እንዲነሳ በመግለጫው አሳስቧል።
መግለጫው አክሎም በትግራይ ህገ መንግስት አንቀፅ 73(2) የሚጻረር በመሆኑ የወረዳ፣ ከተማ፣ ክፍለ ከተማ እና የጣብያ ምክር ቤቶች ተጠያቂነት ስለሆነም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ የምክር ቤቶችን ነፃነትና ሉዓላዊነት እንዲጠብቅ አጽንዖት ሰጥቶ አሳስቧል።
በፕሬዝዳንቱ ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ፤ አዲሱ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ረዳኢ በርሀ ሕጋዊ ያልሆነ ተግባራቸውን እንዲያቆሙ ማሳሰቢያ መስጠታቸው እንዲሁም በመቐለ ከተማ የሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች "ሕጋዊ አይደሉም" የተባሉት ከንቲባ የሚሰጡዋቸው አመራሮች እና ትዕዛዞች ተቀብለው እንዳይፈፅሙም ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አሳሳቢ ችግር ሆኖ መቀጠሉ ተገለጸ
ጥቅምት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ለተፈናቃዮች የሚደረጉ የሰብዓዊ ድጋፍ እና ጥበቃ እንዲሁም የዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ሥራዎችን የሚያስተባበር እና በበላይነት የሚመራ ተቋም ባለመኖሩ፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አሳሳቢ ችግር ሆኖ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመጠበቅ እና ድጋፍ ለማድረግ የወጣውን የካምፓላ ስምምነትን ማጽደቋን ያስታወሰው ኮሚሽኑ፤ "ይህን ስምምነት ለማስፈጸም ብሔራዊ ረቂቅ ሕግ ቢዘጋጅም ጸድቆ ሥራ ላይ ባለመዋሉ የተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አሳሳቢ ሆኗል" ብሏል፡፡
ኢሰመኮ ሦስተኛውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡
ሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በተከናወኑ ክትትሎች እና ምርመራ የተለዩ መልካም ጅማሮዎች፣ አሳሳቢ ጉዳዮች እና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሊተገበሩ የሚገባቸው ምክረ ሐሳቦች በዝርዝር ያካተተ ነው፡፡
በሪፖርቱም 13 የተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትሎች እና 1 ምርመራ በ8 ክልሎች በማከናወን፤ በአጠቃላይ የ333 ሺሕ 889 ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለመፈተሽ መቻሉን ገልጿል።
በዚህም ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው 31 የመጠለያ እና ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያዎችን፣ 13 ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩባቸውን፣ 3 ወደቀድሞ ቀያቸው የተመለሱባቸውን እንዲሁም 3 ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውረው የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች መሸፈኑን አመላክቷል፡፡
ሪፖርቱ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የሆነ የሀገር ውስጥ መፈናቃል ስለመከሰቱን የሚያመላክት መሆኑንም ገልጿል፡፡
በየጊዜው በሚከሰቱ ማንነትን መሠረት ያደረጉ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶች፣ በመንግሥት እና በታጠቁ ቡድኖች መካከል በሚደረጉ ግጭቶች እና ዘላቂ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ መፍትሔ ባልተሰጠባቸው "የወሰን ይገባኛል" ጥያቄዎች ምክንያት በሚከሰት ግጭት እና ጦርነት ለዜጎች መፈናቀል እንደምክንያት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስቷል፡፡
እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች ምክንያቶች በአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ሶማሊ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ የሆኑ በየመጠለያ ጣቢያው እና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደሚገኙም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በግንቦት ወር 2024 ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙ ማስታወቁ ይታወሳል።
ከእነዚህም ውስጥ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን (68.7 ከመቶ) የሚሆኑት በግጭትና ጦርነት፣ 500 ሺሕ (16 ነጥብ 8 ከመቶ) የሚሆኑት በድርቅ ቀሪዎች ደግሞ በሌሎች ምክንያቶች በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ እና በልማት ሥራዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን አመላክቷል።
ከእነዚህም 56 ከመቶ የሚሆኑት ከ1 ዓመት፣ 23 ከመቶ የሚሆኑት ከ2 እስከ 4 ዓመት እና 11 ከመቶ የሚሆኑት ከ5 ዓመት በላይ በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል።
ይህ አኃዝ በአማራ ክልል ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት መረጃ በበቂ ሁኔታ ያልተሰበሰበ በመሆኑ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ኢሰማኮ በሪፖርቱ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መፈናቀል አብዛኛው በግጭት ምክንያት በመሆኑ በመፈናቀል እና በድኅረ መፈናቀል ወቅት ሰዎች ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሲጋለጡ በስፋት እንደሚስተዋልም ገልጿል።
ይህም ሰዎች የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው እንዲሸሹ፣ ንብረታቸው እንዲወድምና እንዲዘረፍ ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ቀዳሚ የሆነውን የሰዎች በሕይወት የመኖር መብትን ጨምሮ አጠቃላይ ሀገራዊ ሰላምና ደኅንነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።
"በኃይል ማፈናቀል በርካታ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋትን የሚያስከትል በመሆኑ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው እንዲሸሹ እና ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው ጥገኝነት እና ድጋፍ እንዲጠይቁ ያስገድዳቸዋል" ተብሏል።
ይህም ተፈናቃዮችን ሞትን ጨምሮ ለተለያዩ አካላዊ ጉዳት የሚዳርግ፣ ያፈሩትን ንብረት እና የገቢ ምንጫቸውን የሚያሳጣ በመሆኑ መሠረታዊ የሆኑትን በሕይወት የመኖር፣ አካላዊ ደኅንነት እና ንብረት የማፍራት መብቶችን እንዲጣሱ ከማድረግ ባለፈ ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች እንደዳረጋቸውም ተገልጿል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የተሟላ ጥበቃ እና ድጋፍ ማረጋገጥ የሁሉንም መንግሥታዊ ተቋማት ትኩረትና ትብብር የሚፈልግ ቢሆንም፤ በዘርፉ የተሰማሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን ለማስተባበር እና ለመምራት በሕግ ግልጽ ሥልጣን የተሰጠው አካል አለመኖሩ፤ ለተፈናቃዮች የተሟላ ድጋፍ እና ጥበቃ ለማድረግ በተሰማሩ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሠራር እንዳይኖር ማድረጉን ኮሚሽኑ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርቱ ልዩ ድጋፍ ለሚስፈልጋቸው ተፈናቃዮች በተለይም ከቤተሰባቸው ለተለዩ እና ጠባቂ ለሌላቸው ሕፃናት፣ ለሴት የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች፣ ለነፍሰጡሮች፣ ጨቅላ ሕፃናት ላሏቸው እናቶች፣ ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች ወይም የማይድን/ቋሚ ሕመም ላለባቸው ተፈናቃዮች ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም ለተፈናቃይ ሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲሁም ወሲባዊ እና ሌሎች ተያያዥ ጥቃቶች ለደረሰባቸው ተገቢው የሥነ ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው አሳስቧል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#አሐዱ_ትንታኔ
ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/ZEfBbE8uXDA?si=1M-SOUzvLl_8k-12
በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 125 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ
ጥቅምት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 125 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጿል።
በዚሁ መሠረት በትናንትው ዕለት 61 እና በዛሬ ዕለት ደግሞ 65 ዜጎች ከሊባኖስ እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቋል፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቤይሩት ከሚገኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን በቀጣይም ሌሎች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎቻችንን ወደ አገራቸው ለመመለስ አስፈላጊውን ጥረት ያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ