በሕገ-ወጥ እርድ የተከናወነ ከ2 ሺሕ 8 መቶ ኪሎ ግራም በላይ ሥጋ መወገዱ ተገለጸ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕገ-ወጥ እርድ የተከናወነ ከ2 ሺሕ 8 መቶ ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ሥጋ ማስወገዱን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታውቋል፡፡
በሦስት ወራት ውስጥ ከ1 መቶ 8 ሺሕ በላይ የእንስሳት እርድ ለማከናወን በእቅድ ተይዞ እንደነበር የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረ ሚካኤል ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"ከእቅዱ ውስጥም ከ1 መቶ 2 ሺሕ በላይ በሚሆኑ እንስሳት ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ እርድ ተከናውኗል" ብለዋል፡፡
ኃላፊው ከአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከአዲስ አበባ አርሶአደር እና ከተማ ግብርና ኮሚሽን እንዲሁም ከሌሎች ጋር በመሆን በሕገ-ወጥ እርድ ላይ የክትትል ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡
በክትትላቸውም የሚያጋጥሙ ሕገ-ወጥ እርዶችን የሚያስወግዱት አሰራር ስለመኖሩ ገልጸው፤ በሦስት ወራት ውስጥ ከ2 ሺሕ 8 መቶ ኪሎግራም በላይ የሚመዝን በሕገ-ወጥ መንገድ የተከናወነ እርድ መወገዱን ጠቁመዋል፡፡
የሩብ ዓመቱ የበዓላት ወቅት እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው፤ የሚከናወነው የእንስሳት እርድ የሚጨምርበት ሁኔታ ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡
ለህብረተሰቡ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመረመረ የእርድ አገልግሎት እንደሚሰጡ የገለጹ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የጨመረበት ሁኔታ መኖሩንም አመላክተዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ!
የክቡር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ አልባሳትና ቁሳቁስ ለዕይታ ሊቀርብ ነው
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ አልባሳት እና ቁሳቁስ ትውልድ እንዲያየው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ተቋም ጥቅምት 29 ቀን 2017 በክብር ይቀመጣል ተባለ፡፡
በዕለቱም የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ አድናቂዎች እና ሌሎች እንግዶች እንደሚገኙ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ የመታሰቢያ ዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴ ለኤፍ ቢ ሲ አስታውቋል፡፡
ታሪካዊ የሆኑ እና በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ኅያው ሆነው እንዲኖሩ ከአርቲስቱ ቤተሰቦች የተሰበሰቡ አልባሳት እና ቁሳቁሶችንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረክቦ ለዕይታ እንዲበቃ በባለቤትነት ይረከባል ተብሏል፡፡
አርቲስቱን የሚያስታውስ የፎቶ ዐውደ-ርዕይ እና ሥራዎች በዕለቱ ለታዳሚያን እንደሚቀርቡም ተጠቁሟል፡፡
ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ከ400 በላይ የሙዚቃ ሥራዎችን ያበረከተ ሲሆን፤ ወደ 40 ከሚጠጉ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች በወሰዳቸው የሙዚቃ ሥራዎቹ ስለፍቅር፣ ስለአገር፣ ስለቤተሰብ፣ ስለፖለቲካ፣ ስለተፈጥሮ ስለማኅበራዊ ጉዳዮች የተጫወተ ታላቅ የሙዚቃ ባለሙያ እንደነበር አይዘነጋም።
ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሚያዚያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ማረፉ ይታወቃል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ!
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ከፍ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጫና የሚቀንስና ካፒታሉን ከፍ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፡፡
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ብድር ባለመመለሳቸውና የብድር ወለዱም በጣም ከፍ በማለቱ በባንኩ ላይ ጫና መፍጠሩን አብራርተው፤ ባንኩ የሀገሪቱ ዋነኛ ተቋም በመሆኑ 900 ቢሊየን ብሩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ሆኖ እንዲከፈል እና መነሻ ካፒታሉም ከፍ እንዲል ውሳኔ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ በቀጥታ ወደ ሁለተኛ ንባብ ተሸጋግሮና ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅም ዶ/ር ተስፋዬ ጠይቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ የቀረበውን ሞሽን የደገፈ ሲሆን፤ በቀጣይ በልማት ድርጅቶች በኩል ያለው አሰራር እንዲፈተሽ በምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
ሞሽኑን አስመልክቶ ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች የገንዘብ ሚንስትሩ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
"ቀደም ባለው ጊዜ የልማት ባንኮች እና የልማት ድርጅቶች ምን አይነት ኪሳራ ላይ ወድቀው እንደነበር የተከበረው ምክር ቤት ያውቀዋል" ያሉት ሚንስትሩ፤ መንግሥት ‹‹ከዕዳ ወደ ምንዳ›› የሚለውን መሪ ቃል መሰረት አድርጎ በሰራው ማሻሻያ በርካታ የልማት ድርጅቶች ከኪሰራ ወደ ትርፋማነት እየተቀየሩ መምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም በልማት ድርጅቶች ላይ የተሻለ ቁጥጥርና ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በመንግሥት በኩል የተወሰደው እርምጃ በመንግሥት ላይ የተወሰነ ጫና የሚያመጣ ቢሆንም፤ ሊደርስ ከሚችለው ከፍተኛ ጉዳት ግን የታደገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1346/2017 ሆኖ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ!
የዛሬ ፕሮግራም ጥቆማ!
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚያዘጋጀውና የሰላም ግንባታ ላይ የሚያተኩረው ልዩ ፕሮግራም ዘወትር ማክሰኞ ከምሽቱ 11፤ 30 ጀምሮ በአሐዱ 94.3 ላይ ወደ እናንተ ውድ ቤተሰቦቻችን ያደርሳል፡፡
ፕሮግራሙን እንድትከታተሉና ሃሳብ እንድታደርሱን በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ፣ ይደውሉልን፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ738 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ብድር ሰጠች
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በአለም አዲስ አገር ለሆነችው ደቡብ ሱዳን፤ በሁለቱ አገራት መካከል አገናኝ ለሚሆን መንገድ ግንባታ የሚውል ብድር መስጠቷ ተነግሯል።
የአራት ዓመት እፎይታ ኖሮት በ10 ዓመታት ተከፍሎ የሚጠናቀቀው ብድር፤ ከ738 ሚሊየን ዶላር በላይ መሆኑም ነው የተነገረው።
በዚህም በደቡብ ሱዳን ድንበር ውስጥ የሚገነባው 220 ኪሜ መንገድ በኢትዮጵያ ተቋራጮች እና አማካሪዎች እንዲከናወን በሁለቱ አገራት ከስምምነት መደረሱን ካፒታል ጋዜጣ አስነብቧል።
የብድር አመላለሱም በጥሬ ገንዘብ እና በድፍድፍ ነዳጅ እንደሚሆን የብድር ሥምምነት ሰነዱ ላይ ተመላክቷል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
"በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት አሜሪካን አሳስቧታል" አንቶኒ ብሊንከን
👉ብሊንከን ግጭቶችን ለመፍታት የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
በውይይታቸውም፤ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያሉ የእርስ በርስ ግጭቶችን ለመፍታት የፖለቲካ ውይይት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ብሊንከን፤ "በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት አሜሪካን አሳስቧታል" ሲሉ መናገራቸውን የጽ/ቤቱ መግለጫ አመላክቷል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀባይ ጽ/ቤት ትናንት ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው በዚሁ መግለጫ፤ አንቶኒ ብሊንከን ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በስልክ የተወያዩት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በፕሪቶርያ ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት እንደነበር ገልጿል፡፡
በዚህም፤ "ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲደረግ ለምታደርገው ጥረት አሜሪካ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ናት" ሲሉ ብሊንከን መናገራቸውን መግለጫው አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም፤ በአፍሪካ ቀንድ እየተካረረ በመጣው ውጥረት ዙሪያም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን መወያየታቸውን ቃል አቀባይ ጽ/ቤቱ አስታውቋል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በአማራ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ ተኩስ አቁም ማድረግ አለበት ሲሉ ፓርቲዎች ገለጹ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በየዕለቱ እየተከሰተ ያለዉን የሕጻናትና እናቶችን ሞት ለማስቆም፤ የፌደራሉ መንግሥት ቁርጠኛ በመሆን የተኩስ አቁም ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ፓርቲዎች ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ ለሰላም ቁርጠኝነት እንዳለ በመግለጽ "አግዙን" ሲሉ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡
አሐዱም ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር መነሻ በማድረግ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን "መንግሥት እውነት ቁርጠኛ ነው ወይ?" ሲል ጠይቋል፡፡
የእናት ፓርቲ አባል አቶ ጌትነት ወርቁ "መንግሥት የተኩስ አቁም ማድረግ አለበት" ያሉ ሲሆን፤ 'ቁርጠኛ መሆን አለበት' ሲባልም "በሌላው ወገን ያሉትም ጦር በማዉረድ ወደ ሌላ አሸናፊ መንገድ ለመምጣት ቁርጠኛ መሆን አለባቸው" ብለዋል፡፡
"መንግሥት ለሰላም ቁርጠኛ ነኝ እያለ ይናገር እንጂ በእውነት መሬት ላይ የወረደ የተተገበረ ነገር ግን ማግኘት አይቻልም" ያሉት ደግሞ፤ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የአደረጃጀትና አቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙባረክ ረሽድ ናቸው፡፡
"አሁንም ግጭት ውስጥ ነው የምንገኘው" ያሉት አቶ ሙባረክ፤ "ለሰላም ዝግጁ የሆነ አካል ቢያንስ ወደ ሰላም የሚያመጡ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አለበት" ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሰላም ፍላጎት መታየቱ በራሱ ግን የሚያስደስትና አንድ ደረጃ ችግሩን አምኖ የሰላም ጥሪ ማድረጉ በበጎ የሚወሰድ መሆኑን ፓርቲዎቹ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥሪያቸው 'እናንተም አግዙ' የሚል ጥሪ ስለማድረጋቸው በሚመለከት ሀሳባቸውን የሰጡት ፓርቲዎቹ፤ "ችግሩ ከእኛም ከመንግሥትም በላይ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም ፀጥታ ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ መንግሥታቸው "ከኃይል ይልቅ ሰላም እጅግ በጣም አዋጭ ነው" ብሎ እንደሚያምን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም ሆኖ ሊቋቋም ይገባል ተባለ
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ያለውን የፍትህ ስርአት ሚዛናዊና ተቋማዊ እንዲሆን ካስፈለገ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ከፍትሕ ሚኒስቴር ተነጥሎ ራሱን መቻል አለበት ሲሉ የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ባለሙያዎቹ ጠቅላይ "ዐቃቢ ሕግ ራሱን የቻለ ተቋም ሆኖ መቋቋም ባለመቻሉ የፍትሕ ስርዓቱ እንዳይፀናና ተአማኒ ተቋም እንዳይሆን እያረገው ይገኛል" ሲሉም ለአሐዱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ራሱን የቻለ ተቋም ሆኖ እንዲቋቋምና ከፓለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆኑ ባለሙያዎች እንዲመራ ውትወታ ሲደረግ መቆየቱን ለአሐዱ ያስታወሱት፤ የሕግ ባለሙያው አቶ ታምራት ኪዳነማርያም ናቸው፡፡
ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ራሱን ችሎ መቆም ባለመቻሉና የፍትሕ ሚኒስቴር ጥገኛ እንዲሆን በመደረጉ ምክንያትም የፍትህ ስርአቱና የሕግ የበላይነት እንዲሸረሸር አድርጎታል ባይ ናቸው።
'የፍትህ ስርአቱ ገለልተኛ ነው' ማለት የሚቻለው፤ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ከፍትሕ ሚኒስቴር ተነጥሎ መውጣት ሲችልና ራሱን በራሱ ሲመራ ብቻ መሆኑንም አቶ ታምራት ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የፍትህ ስርአቱ መዛባት፤ የገለልተኝነት ጥያቄ ባለመፈታቱ ምክንያት የመጣ መሆኑንም አንስተዋል።
ሌላኛው በዚሁ ዙርያ ሐሳባቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያ ደበበ ወልደገብርኤል በበኩላቸው፤ "በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት እንዳይኖር ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የፍትሕ ስርአቱ ከፓለቲካ ጣልቃ ገብነትና ጫና መላቀቅ አለመቻሉ ነው" ብለዋል፡፡
ባለሙያው አክለውም፤ የፍትሕ ሚኒስቴር የፓለቲካ ተቋም እንደመሆኑ መጠን በፍትሕ ስርአቱ ላይ ገለልተኛ ነው ብሎ መውሰድ እንደማይቻል ነግረውናል።
"የፍትህ ሚኒስቴር በአገሪቱ ለፍትሕ መዛባትና በሕግ ላይ ተአማኒነት ማጣት ምክንያትም፤ ከሚኒስቴሩ እጅ ወጥተው በገለልተኛ ተቋም መተዳደር የነበረባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
"በአገር ውስጥ ያለውን የፍትህ ስርአት የተስተካከለ እንዲሆን ከተፈለገ፤ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በሚገባ ማጤን ይኖርባቸዋል" ሲሉም ባለሙያዎቹ ለአሐዱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአማኑዔል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የአቅም ማሻሻያ (Remedial) ፕሮግራም ምደባ ይፋ ተደረገ
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2016 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ አገር አቀፍ ፈተና ወስደው ለትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ በሆኑ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች የREMEDIAL ፕሮግራም ለመከታተል የሚያስችል ማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የተቋም ምደባ ይፋ ተደርጓል።
በዚህም መሰረት ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ከታች በተዘረዘሩት አማራጮች ምደባቸውን ማየት የሚችሉ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ስለዚህም ተማሪዎች፡-
Website: https://placement.ethernet.edu.et
Telegram: /channel/moestudentbot ላይ ምደባውን መመልከት ይችላሉ ተብሏል፡፡
ተማሪዎች ተቋማት በሚያስተላልፉት ጥሪ መሰረት የአቅም ማሻሻያ (Remedial) ፕሮግራሙን እንዲከታተሉ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ የሚገኙ መምህራን ከ2 ወር በላይ ደምወዞ ስላልተከፈላቸው ለተለያየ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን ገለጹ
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ የመምህራን ደምወዝ ከ2 ወር በላይ ባለመከፈሉ ምክንያት፤ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑን የአካባቢው መምህራን ለአሐዱ ቅሬታቸዉን አሰምተዋል።
በአካባቢው ባለው የጸጥታዉ ችግር ምክንያት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የገለጹት መምህራኑ፤ ከመስከረም ወር 2017 ጀምሮ ደምወዝ እየተከፈላቸዉ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚተዳደሩት በማስተማር በሚያገኙት የወር ደሞዛቸዉ ብቻ በመሆኑ ደምወዛቸዉ ሲቋረጥ ልጆጃቸዉን ለማስተዳደና የዕለት ጉርስ ለማግኘት መቸገራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የመምህራንን ደሞዝ ማቋረጡ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በአካባቢዉ የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን እንዲከፈቱና የመምህራን ደምወዝ እንዲከፈላቸዉም ለሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
አክለዉም የደሞዝ ክፍያን በተመለከተ የሚመለከተዉን አካል ሲይቁ፤ "ትምህርት ቤቶች ስለተዘጉ እናንተም ሳታስተምሩ ደሞዝ አይከፈላችሁም" የሚል ምላሽ እንደሰጧቸዉ ተናግረዋል።
ደሞዝ ያልተከፈላቸዉ መምህራን እንደ አጠቃላይ በግምት ከ700 በላይ እንደሚሆኑም ለአሐዱ ገልጸዋል።
አሐዱም ይህንን ችግር በተመለከተ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን ለማነጋገር ያደረገዉ ጥረት አልተሳካም። ምላሹን እንዳገኘን ወደእናንተ የምናደርስ ይሆናል።
በአለምነው ሹሙ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በኢትዮጵያ 22 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት ከትምህርታቸው ወደኋላ እንደሚቀሩ ተገለጸ
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ 22 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ መገለሎች ምክንያት ከትምህርታቸው ወደኋላ እንደሚቀሩ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት አስታውቋል፡፡
የሴቶች ማህበራት ቅንጅቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ እንዲሁም ትግራይን ጨምሮ በሌሎች አምስት ክልልሎች የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና እና ተሳትፎን በሚመለከት የተጠናዉን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
ጥናቱ በስምንት ክልሎች ለ26 ወራት የተደረገ ሲሆን፤ በሁሉም ክልሎች በአጠቃላይ ከ36 ሺሕ በላይ ሴቶች ተሳታፊ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
በጥናቱ አሁናዊ የፖለቲካ እና ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ጫናዎችን በሚመለከት ሰፊ ዳሰሳ ተደርጓል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ 22 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በሚደርስባቸው የተለያዩ መገለሎች ምክንያት ከትምህርታቸው ወደኋላ እንደሚቀሩ መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
የጥናቱ ግኝቶች የሴቶችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ያለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት ፋይዳ እንዳለው የተመላከተ ሲሆን፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህንን ክፍተት ለመሙላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ይህ ተግባራዊ ጥናት መደረጉ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚታዩ የፖሊሲ ክፍተቶችን ለማስተካከል እና አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ ተብሏል፡፡
ጥናቱን ላለፉት 2 ዓመታት የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት፣ ኦክስፋም ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ልዑካን በጋራ ማከናወናቸው ተገልጿል።
በፅዮን ይልማ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በመዲኗ በሩብ ዓመቱ ከ42 ሚሊየን ብር በላይ ከደንብ መተላለፍ ቅጣት መገኘቱ ተገለጸ
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተያዘው በጀት ዓመት የሩብ ዓመት አፈጻጸም ከኮሪደር ልማት እንዲሁም ከሌሎች ደንብ መተላለፎች፤ ከ42 ሚሊየን ብር በላይ መቅጣቱን የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታውቋል።
ባለስልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የተከናወኑ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እና የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ ባካሄደው መድረክ ላይ ነው ይህንን የገለጸው።
በ2016 በጀት ዓመት በአጠቃላይ በዓመቱ ከደንብ መተላለፍ 66 ሚሊየን ብር መገኘቱን የገለጸው ባለስልጣኑ፤ በዚህ ሩብ ዓመት ግን ከ42 ሚሊየን ብር በቅጣት መሰብሰቡን ገልጿል።
ለዚህም በተያዘው ዓመት የቁጥጥር መጥበቁ ማሳያ መሆኑን አንስቶ፤ ከቅጣት የተሰበሰበውን ገንዘብ ለከተማ አስተዳደሩ ገቢ ተደርጓል ብሏል።
በተመሳሳይ በሩብ ዓመቱ ሕገ-ወጥ የጎዳና ንግድ፣ ሕገወጥ ግንባታዎች፣ የመሬት ወረራን ጨምሮ የተያዩ የደንብ መተላለፎች እንደነበሩ ተገልጿል።
በፍርቱና ወልደአብ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#ADVERTISMENT
#ጊፍትሪልስቴት
ታላቅ የምስራች!
**************
ጊፍት ሪል ስቴት ከ10% ቅድመ ክፍያ ጀምሮ በ22 ሳይቶቹ ቅንጡ አፓርትመንቶችን እና የንግድ ሱቆችን ለሽያጭ አቅርቧል፡፡
ይህ ሳይት ለአፓርትመንትና ንግድ ሱቆች የሚውሉ G+25 ሶስት መንታ ህንጻዎች ያሉት ሲሆን የዚህ 6ኛ መንደር መለያዎች፡-
•ከባለአንድ እስከ ባለአራት መኝታ ክፍሎች ያሉት፣
•ለመኖሪያም ሆነ ለንግድ ተመራጭ አካባቢ የሆነ፣
•በአንድ ወለል ሶስት ቤቶች ብቻ ያሉት፣
•በእያንዳንዱ ወለል ስድስት አሳንስር ያለው፣
•አራት ቤዝመንት ያሉት በቂ የመኪና ማቆሚያ የተዘጋጀለት፣
•24 ሰዓት የኤሌክትሪክ፣ ኢንተርኔትና ውሃ አቅርቦት አሉት፣
ጊፍት ሪል ስቴት
ማህበረሰብን እንገነባለን!
ለበለጠ መረጃ፡-
Website: https://www.giftbusinessgroup.com
Twitter: https://twitter.com/GIFTBusinessG
YouTube: www.youtube.com/channel/UCcqr7cpVv9ski-F7haxXx4w
Facebook: www.facebook.com/profile.php?id=100090918391017...
Telegram: /channel/giftbusinessgroup
Short Code: 8055
#አሐዱ_ትንታኔ
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ አለዛም የዲሞክራቱዋ ካማላ ሀሪስ ኋይት ሀውስ ቢገቡ፤ አሜሪካ ብሎም የተቀረው አለም ምን አይነት ለውጦችን ሊያስተናግድ ይችላል የሚለው የዛሬ አለማቀፍ ትንታኔ ትኩረታችን ነው፡፡
ሙሉ ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/DsqfHCyTqh8?si=ugNHIkKIuyciNtA7
የኢነርጂ ስርቆት ላይ የተሰማሩ ሕገ-ወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተበራከቱ መምጣታቸው ተገለጸ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኢነርጂ ስርቆት ላይ የተሰማሩ ሕገ-ወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተበራከቱ መምጣታቸውን አስታውቋል።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በተገዙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ስርቆትና ውድመት በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሉታዊ ተፅኖ የሚያሳድር እንደመሆኑ ልዩ ትኩረትን የሚሻ መሆኑን ነው ተቋሙ የገለጸው።
"ከብዙኃን ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም የኃይል ማሰራጫ መስመሮች ላይ የስርቆት ወንጀል የሚፈጽሙና ጉዳት የሚፈፅሙ ብሎም፤ የሃይል ስርቆት ላይ የተሰማሩ ሕገ-ወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል" ብሏል፡፡
ይህም ተቋሙ የተቋቋመበትን ዋነኛ አላማ በአግባቡ እንዳይወጣ መሰል ሕገ-ወጥ ተግባራት ተፅዕኖ ከማሳደራቸው ባሻገር፤ "ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በሚፈልገው ደረጃ እንዳያገኝ ጫና በማሳደር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል" ሲል ገልጿል፡፡
"በበጀት ዓመቱ 3 ወራት ብቻ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ባላቸው መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት ተፈፅሞብኛል" ያለው ተቋሙ፤ ባለፈው ዓመት በተፈጸሙ 155 የስርቆት ወንጀሎች ከ52 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቋል፡፡
በእነዚህ ወንጀሎቹ ተሳትፈዋል ተብለው ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠባቸው 57 ሰዎች ከአምስት ወር እስከ 18 ዓመት እስራት መቀጣታቸውንም ገልጿል፡፡
"የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለአገሪቷ ወሳኝ ሚና ያለው ከመሆኑ የተነሳ መሰረተ ልማቱን ለማስፋፋት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ይደረጋል" ነው ያለው ተቋሙ፡፡
በዚህም የኤሌክትሪክ መስመሮች በባህሪያቸው ለጥቃት ድርጊት የተጋለጡና አገልግሎቱ ለአፍታ እንኳን ቢቋረጥ በብሄራዊ ኢኮኖሚ ደህንነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 55/1 ላይ ልዩ ጥበቃ እንደሚያስፈልግ መቀመጡን አንስቷል።
ከዚህ በተጨማሪም በቴሌ ኮሚኒኬሽንና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 464/97 መሰረት፤ በሕግ የሚያስቀጣ እንደሆነ መደንገጉን ገልጿል፡፡
በመሆኑም "አዋጁን ተላልፎ ድርጊቱን የፈጸመ ማንኛውም አካል ላይ፤ ከ5 ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ በግልፅ ተቀምጧል" ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳስቧል።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ!
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ዝንባሌ ያላቸው ሰልጣኞች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መመሪያ መሰጠቱ ተገለጸ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ዝንባሌ ያላቸው ሰልጣኞች ላይ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ መመሪያ መሰጠቱን የቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ኢንስቲትዩቱ የያዘው ውጥን እንዲሰምር ከተለያዩ በግሉ ዘርፍ ያሉ የቴክኖሎጂ አገልግሎት አበልፃጊ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት እቅድ መያዙን አስታውቋል።
በዛሬው ዕለትም የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶልሽንስ ከተሰኘ ቴክኖሎጂ አበልፃጊ ድርጅት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ውል አስረዋል።
ስምምነቱ የተሻለ የአገልግሎት ኢንዱስትሪን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው የገለጹት፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ከድር ናቸው።
በአዲሱ በጀት ዓመትም በቴክኒክና ሙያ ስልጠና የትምህርት ተቋማትና በኢትዮጵያ ያሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር በትብብር እንዲሰሩ መንግሥት መመርያ መስጠቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት "ከመንግሥት በቀረበው ጥሪ መሰረት አሸዋ ቴክኖሎጂስ ሶልሽን ኢንስቲትዩት ቀዳሚው የቴክኖሎጂ አበልፃጊ ድርጅት መሆን ችሏል" ተብሏል።
የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶልሽንስ ሥራ አስኪያጅ ዳንኤል በቀለ በኩላቸው፤ የመንግሥት ተቋማት የሚያሰለጥኗቸው ሙያተኞችን ገበያው በሚፈልገው ልክ እንዲበቁ ድርጅታቸው እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በቀረበው የትብብር መስክ መሰረት ጥሪ እየተደረገላቸው መሆኑን ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ከድር ሰምተናል።
በአማኑዔል ክንደያ
በኢትዮጵያ ከ600 ሺሕ በላይ ሕጻናት በዘመናዊ ባርነት ውስጥ እንደሚገኙ ተገለጸ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ከስድስት መቶ 14 ሺሕ ያላነሱ ሕጻናት የዘመናዊ ባርነት ሰለባ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመላክቷል።
ጥናቱ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ከስዊዘርላንድ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የቀረበ ነው።
በዚህም ሕጻናት የዘመናዊ ባርነት ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ የጸጥታ አካላት እንዲሁም በየአካባቢያቸው ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደሚሳተፉበት በጥናቱ ተገልጿል፡፡
ዘመናዊ ባርነት አሁን ላይ አይነቱን እየቀየረና እየተባባሰ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ ጥናቱ እንደሚያሳየው ከሆነ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ስደተኞችን ተቀባይ ሀገር ብትሆንም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምንጭ፣ መተላለፊያ እና መዳረሻ ናት።
በዚህ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በተለይም በሕጻናት ዘመናዊ ባርነት፤ ከ1 ሺሕ ሕጻናት ውስጥ 6 ሕጻናት ለዘመናዊ ባርነት ማለትም ለወሲብ ንግድ፣ ለአካል ክፍል ሽያጭ እና ለሌሎች ችግሮች የተጋለጡ ናቸው ተብሏል።
በተለይም ከሳውድ አረቢያ፣ ከየመንና፣ ከሱዳን የሚመለሱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተመላሽ ዜጎች ለሕገ-ወጥ ዝውውሩ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል።
በእመቤት ሲሳይ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በመዲናዋ በሩብ ዓመቱ በተከለከሉ ሥፍራዎች አላግባብ ቆሻሻዎችን በሚጥሉ 2 ሺሕ 722 ነዋሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በ2017 ዓ.ም የሩብ ዓመቱ አላግባብ በተከለከሉ ሥፍራዎች ላይ ፈስሻ እና ደረቅ ቆሻሻዎችን ሲያስወግዱ የተገኙ 2ሺሕ 722 ነዋሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታውቋል።
ባለሥልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተሰሩ የልማት ኮሪደር እና የመደበኛ የቅድመ መከላከል እና እርምጃዎች አወሳሰድ ሥራዎችን በተመለከተ፤ የከተማዋ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የከተማዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና የማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት እያካሄደው በሚገኘው መድረክ ላይ ነው ይህንን የተናገረው ።
በዚህም የገንዘብ ቅጣት እና ሌሎች መሰል እርምጃዎች መወሰዳቸው የተነገረ ሲሆን፤ ደምብ ማስከበር ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ በከተማዋ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ደምብ መተላለፎች መቀረፋቸውን በመድረኩ ተነስቷል።
ከተወሰዱት እርምጃዎች በፊት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት መሰራቱንም ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
ባልሥልጣኑ በ2016 በጀት ዓመት በአጠቃላይ በዓመቱ ከደንብ መተላለፍ 66 ሚሊዮን ብር መገኘቱን የገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ሩብ ዓመት ደግሞ 42 ሚሊዮን ብር በቅጣት መሰብሰቡን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል።
በወልደሀዋርያት ዘነበ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#UPDATE
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላ ተረከበ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን በፈረንሳይ ቱሉዝ በተካሄደ ሥነ ስርዓት ከኤርባስ ኩባንያ መረከቡን አስታውቋል።
በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲ ለሚክ እንዲሁም የኤርባስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡
ይህ የተረከበው ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ እንደሚገባም አየር መንገዱ አስታውቋል።
ለደንበኞች የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ይህ አውሮፕላን፤ 46 የቢዝነስ ደረጃ እና 349 የኢኮኖሚ ደረጃ መቀመጫዎች በአጠቃላይ 395 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፤ "Ethiopia land of origins" የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#ADVERTISMENT
#AhaduBank
🔊ለአሐዱ፡ባንክ አ.ማ. ባለአክሲዮኖች በሙሉ
የባለአክሲዮኖች 3ተኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ፤ ሚኒሊየም አዳራሽ ይካሄዳል።
በመሆኑም የባንኩ ባለአክሲዮኖች ወይም ህጋዊ ወኪሎቻቸው በተጠቀሰው ቀን፣ ሰዓት እና ቦታ በጉባዔው ላይ እንዲገኙ የዳይሬክተሮች ቦርድ በአክብሮት ጥሪውን ያስተላልፋል።
አሐዱ፡ባንክ
ከብዙዎች ለብዙዎች
የአሐዱ፡ባንክ ማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ
👉https://linktr.ee/Ahadu_Bank
#አሐዱ_አንቀፅ
በሕግ እና ሥርዓት የማይመራ እና የማይተዳደር ሀገር እና ህዝብ የስርዓት አልበኞችና የጉልበተኞች መፈንጫ ከመሆን አይድንም!
ሙሉ ጥንቅሩን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/jYd8Zpq7r-c?si=MMYBOwJLcLcYzXTc
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው ዕለት 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ በነገው ዕለት ይካሄዳል፡፡
ምክር ቤቱ ነገ በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል የፌዴራል የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራት ምክር ቤቱ በነገው መደበኛ ስብሰባ የሚወያይበት ሌላኛው አጀንዳ መሆኑን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#UPDATE
ተቋርጦ የነበረው የድሬዳዋ ሀረር እና ሱማሌ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ ጀመረ
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጥቅምት 23 ቀን 2017 በእሳት አደጋ ምክንያት በጊዜያዊነት አገልግሎት መስጠት ያቋረጠውን የድሬዳዋ ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ መስመር የማዛወር ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታውቋል፡፡
በዘርፉ የምስራቅ አንድ ሪጅን የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ወርዲ መሀመድ፤ ትናንት ምሽት ከ1:00 ሰዓት እስከ ሌሊት 11፡00 ከሁርሶ ወደ ድሬዳዋ አንድ፣ ወደ ሀረር እና ጅግጅጋ የሚሄዱ መስመሮችን የማዛወር ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡
በዚህም መሰረት ዛሬ ረፋድ መስመሩን የመፈተሽ ሥራ ተከናውኖ ወደሁሉም አካባቢዎች ኃይል እንደደረሰ መረጋገጡን ተናግረዋል።
የሁርሶ ማከፋፈያ ጣቢያ ጉዳት እንዳጋጠመው ተደርጎ የተሰራጨው ዘገባ የሀሰት መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ከሁርሶ ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ ወጪ መስመር በማዘጋጀት ችግሩ መፈታቱን አስታውቀዋል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#አሐዱ_ትንታኔ
በመላው አሜሪካ እየተጠበቀ ያለው ደግሞም የአሜሪካን ግዙፍ ፓርቲዎች ማለትም ሪፐብሊካንን እና ዲሞክራትን ፊት ለፊት የሚያፋጥጠው ምርጫ በነገው ዕለት ይካሄዳል፡፡
የፕላኔቷ ልዕለ ሃያል ሀገር አሜሪካን ቀጣይ አራት ዓመታት እጣ ፈንታ ለመወሰን ሥልጣነ መንበሩን ከተሰናባቹ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ማን ይረከባል? የሚለው ጥያቄ፤ በነገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ምላሽ ያገኛል፡፡
ይህን የአሜሪካን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ሀገራት ዕጣ ፈንታ የመበየን አቅም ያለውን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እና የእስከአሁን የቅድመ ምርጫ ቀን ድምጽ ውጤት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በዛሬው የአለም አቀፍ ትንታኔያችን ተመልክተነዋል፡፡
ሙሉ ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/yQJyOB4j57Q?si=5yw9CFtntv1i1U2E
ሶማሊያ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ከፕሬዝዳንቱ ቅጥር ግቢ ልታስወጣ መሆኑን ገለጸች
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ በአሁኑ ወቅት በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ ሌላ ባዶ ቦታ ለማዘዋወር መታቀዱን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ ትናንት ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ለሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ "ውሳኔው የተወሰነው በፕሬዝዳንቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የውጭ ሀገር ኤምባሲ መገኘቱ፤ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ማስነሳቱን ተከትሎ ነው" ብለዋል።
"የሶማሊያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚገኝበት ቦታ ላይ ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ ነው።" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ውጭ ወደሚገኝ አዲስ ቦታ እንዲዛወር ለማድረግ ፈጣን እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም "ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይገኝበት የነበረው አከባቢ በአሁኑ ሰአት ምንም አይነት ጥቅም እየሰጠ አይደለም፤ እሱን አድሰን ኤምባሲው ወደዚያው እንዲዛወር እናደርጋለን" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህ ካልሆነ ግን በተመሳሳይ "በአዲሰ አበባ የሚገኘውን የሶማሊያ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ግቢ ውስጥ እንዲሆን የሚል ጥያቄ እናቀርባለን" በማለት ተናግረዋል።
ይህ እርምጃ በፕሬዝዳንት አብዱላሂ ዩሱፍ አህመድ መንግሥት ፍቃድ ተሰጥቶታልም ተብሏል።
ይህ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጫ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነትን መፈራረሟን ተከትሎ፤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል እየተካረረ የመጣውን ልዩነት የሚያንጸባርቅ መሆኑ ተዘግቧል።
ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ በአማካሪነት የሚሰሩት አሊ መሀመድ አደም "ከዲፕሎማሲ ሥራዎች የሚጣረስ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው ተገኝተዋል" በሚል፤ በ72 ሰዓት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በሚኒስቴሩ መታዛቸውን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ሱዳን የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ቀይ ባሕር ላይ አዲስ ወደብ እንድትገነባ የተደረሰውን የ6 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መሰረዟን አስታወቀች
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሱዳን ቀይ ባህር ላይ አዲስ ወደብ እንድትገነባ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር የገባቸውን የ6 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መሰረዟን የሀገሪቱ ገንዘብ ሚኒስትር ጂብሪል ኢብራሂም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ "አቡ ዳቢ በሀገሪቱ እየተከሰተ ባለው ግጭት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርን ትደግፋለች" ሲሉ ከሰዋል።
እ.ኤ.አ በታህሳስ 2022 የተፈረመው ስምምነት አቡዳቢ ከፖርት ሱዳን በስተሰሜን 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የአቡ አማማ ወደብን በ6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት እና ለማስተዳደር የሚፈቅድ ነበር፡፡
ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፤ እ.ኤ.አ "ከታህሳስ 15 ጀምሮ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጋ ላለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ድጋፍ ሰጥታለች" ያሉ ሲሆን፤ "ይህ ከሆነ በኋላ ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ አንድ ሴንቲሜትር አንሰጥም" ብለዋል።
የተሰረዘው ፕሮጀክት ወደቡ በሚገነባበት አካባቢ ነጻ የንግድ ቀጠና ማቋቋም፣ የግብርና ፕሮጀክት እና ለሱዳን ማዕከላዊ ባንክ የ300 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ገንዘብ ያካተተ ፕሮጀክት እንደነበር የሱዳን ትሪቡን ዘገባ አመላክቷል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን በነገው ዕለት አዲስ አበባ ይገባል
ጥቅምት 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን፤ በነገው ዕለት አዲስ አበባ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል፡፡
አየር መንገዱ ኤ350-1000 "Ethiopia land of origins" የተሰኘ የመንገደኞች አውሮፕላን ከኤር ባስ ኩባንያ በቅርቡ እንደሚረከብ መግለጹ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያም፤ አየር መንገዱ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን ተናግረዋል።
በተጨማሪም አየር መንገዱ በዓመት እስከ 130 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን በማብራሪያቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በትናንትናው ዕለት በኢፌዲሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የተመራ ልዑክ ኤር ባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላንን ለመረከብ ፈረንሳይ ገብቷል፡፡
ልዑካን ቡድኑ ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እና ሌሎች የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት በነገው ዕለት አዲስ አበባ የሚገባው ኤ350-1000 አውሮፕላን፤ "በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንደስትሪ ታሪክ የቀዳሚነታችን ማሳያ ከሆኑት ስኬቶች አንዱ ይሆናል" ሲል አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡
ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላ ለደንበኞች የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሲሆን፤ 46 የቢዝነስ ደረጃ እና 349 የኢኮኖሚ ደረጃ መቀመጫዎች በአጠቃላይ 395 መቀመጫዎች አሉት፡፡
ከሌሎች አውሮፕላኖች ጋር ሲወዳደርም ከፍተኛ የቢዝነስ ደረጃ መቀመጫዎችን ያሉት መሆኑ ተመላክቷል።
በዚህም መሰረት ኤ350-1000 የመጀመሪያ በረራውን ከአዲስ አበባ ወደ ሄትሮው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሕዳር 3 ቀን 2024 በማድረግ ሥራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚመጠበቅ መገለጹን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2035 በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሰራ እንደሚገኝ ያስታወቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ባሉት 147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
እስካሁን በበቂ ሁኔታ ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም ሲሉ የጎፋ ዞን ተፈናቃዮች ገለጹ
ጥቅምት 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት ናዳ፤ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውና ከቀያቸው መፈናቀላቸው አይዘነጋም።
አሐዱም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የአደጋው ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎችን ያሉበትን ሁኔታ ጠይቋል።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ ከሆነ ቃል ከተገባላቸው ውሰጥ ተግባራዊ የተደረገው ጥቂቱ ብቻ ነው ብለዋል። በተጨማሪም "የተደረገው እርዳታ በቂ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"የመሬት መንሸራተቱን ተከትሎ አዲስ ወደ ተገነባልን መኖሪያ ቤት ከተሸጋግረን በኋላም እርዳታ የተደረገልን አንዴ ብቻ ነው። እሱም አጥጋቢ አይደለም" ሲሉም አቤቱታቸውን ለአሐዱ አሰምተዋል።
አክለውም "አሁንም የሰብአዊ ዕርዳታዎች ያስፈልጉናል" ብለዋል።
አሐዱም የነዋሪዎችን ቅሬታ ተቀብሎ የዞኑን የመንግሥት ኮምኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ካሳሁን
አባይነህን ጠይቋል።
ኃላፊው በሰጡት ምላሽም ድጋፉ በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ ሆኖም ከ300 በላይ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው መሰጠታቸውን እንዲሁም የሰብአዊ እና ቁሳዊ እርዳታዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
የመምሪያው ኃላፊ አያይዘውም ከፌደራል ተቋማት ጋር በመሆን ተፈናቃዮቹ በቋሚነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የገለጹ ሲሆን፤ "በቅርቡ ሙሉ በሙሉ የማቋቋም ሥራዎች ይሰራሉ" ብለዋል።
ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በዞኑ የደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሴትችና ሕጻናትን ጨምሮ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ እንዲሁም ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል።
አደጋውን ተከትሎም በርካታ ግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ተቋማት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። ነገር ግን ይህ የተደረው ድጋፍ አሁንም በቂ አለመሆኑን ነው ተፈናቃዮቹ ለአሐዱ የገለጹት።
በወልደሀዋርያት ዘነበ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ