ቴግሬቶል የተሰኘ በአፍ የሚወሰድ ፈሳሽ መድኃኒት ጨቅላ ሕጻናት እንዳይጠቀሙት ማሳሰቢያ ተሰጠ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ቴግሬቶል የተሰኘ በአፍ የሚወሰድ ፈሳሽ (Oral Suspension) መድኃኒት ጨቅላ ሕጻናት እንዳይጠቀሙት የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አሳስቧል።
ቴግሬቶል የተሰኘ በአፍ የሚወሰድ ፈሳሽ (Oral Suspension) መድኃኒት ኖቫርቲስ ፋርማ ሽዌይዝ AG/ Novartis Pharma Schweiz AG በተባለ የገበያ ፍቃድ ባለው የመድኃኒት አምራች ፋብሪካ የሚመረት ነው።
ቴግሬቶል (ካርባማዜፔይን) 100 mg/5ml Oral Suspension (OS) የተሰኘው መድኃኒት አብዛኛውን ጊዜ አጠቃላይ ለሚጥልና ከፊል መንቀጥቀጥ/ management of generalized tonic clonic and partial seizures ለማከም የሚያገለግል መሆኑንም ባለስልጣኑ ገልጿል።
ነገር ግን መድኃኒቱ በውስጡ በሚይዘው ፕሮፓይሊን ግላይኮል (propylene glycol) የሚባል ንጥረ-ነገር መጠን ምክንያት፤ ለጨቅላ ሕጻናት ማለትም ከ4 ሳምንታት በታች ለሆኑ ሕፃናት ወይም በሦስት ወራት የመወለድ ጊዜያቸው ሳይደርስ ለተወለዱ ሕጻናት ሊወስዱት እንደማይመከር ማሳሰቢያ ተላልፏል
በዚህ ምርት ውስጥ ከሚገኙት ተጨማሪ ንጥረ ነገሮች አንዱ የሆነው ፕሮፓይሊን ግላይኮል ለምግብ እና ትንባሆ ምርቶች እንዲሁም ለፋርማሲዩቲካል እና መዋቢያዎች በአጠቃላይ በአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር (FDA) ደህንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ ባለስልጣኑ ገልጿል።
ነገር ግን በዚህ ምርት ውስጥ ያለው መጠን በዚህ የማሳወቂያ መልዕክት ላይ ከተጠቀሱት ለጨቅላ ሕፃናት እና ጊዜያቸው ሳይደርስ ለተወለዱ ሕፃናት እስከ ሦስት ወር ድረስ ከደህንነት ገደብ በላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ነው ያለው።
ስለሆነም ይህንን መድኃኒት በጨቅላ ሕፃናት ጊዜያቸው ሳይደርስ ለተወለዱ ሕፃናት እስከ ሦስት ወር ድረስ መጠቀም ጉዳቱ ከጥቅሙ የሚያመዝን በመሆኑ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች መድኃኒቱን ለተጠቀሱት የእድሜ ክልል ከማዘዝ እና ከማከፋፈል እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ መድኃኒቱን እንዳይጠቀም መልዕክት አስተላልፏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
#አሐዱ_ትንታኔ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንትና የሪፐብሊካኑ እጩ ተፎካካሪ ዶናልድ ትራምፕ የ2024ቱን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ፤ በርካታ የአለም ሀገራት መሪዎች ያልተጠበቀ ድጋፍ እና ነቀፌታን ሰጥተዋቸዋል፡፡
ለመሆኑ የትኞቹ የአለም ሀገራት መሪዎች ለትራምፕ ማሸነፍ ድጋፍ ሰጡ፤ የትኞቹስ ተቃወሙት የሚሉትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በዛሬው የአለም አቀፍ ትንታኔያችን ተመልክተነዋል፡፡
ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/PkD2TaxpXnc?si=BQwGfDKa6dZIKB6E
ለሸኔ ቡድን ሊተላለፍ የነበረ የመገናኛ ራዲዮ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ)በ6ኛ ዕዝ የአንድ ኮር አባላት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ለተፈረጀው እና በኦሮሚያ ክልል በስፋት ለሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን ሊተላለፉ የነበሩ የመገናኛ ራዲዮኖችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል፡፡
መነሻውን አዲስ አበባ አድርጎ አሊ ዲሮ ወደተባለ ቦታ ለቡድኑ ሊደርስ የነበረ 21 ዘመናዊ የመገናኛ ራዲዮን በሰሜን ሸዋ ዞን ፊቼ ከተማ የኮሩ አባላት ባደረጉት ብርቱ ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን የኮሩ ዘመቻ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ጌታሁን ደምሴ ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በወሊሶ ወረዳ ቀብሮት የነበረ 02 ክላሽ ከ280 ጥይት ጋር በተመሳሳይ ጥቆማ መያዙን የተናገሩት ኃላፊው፤ በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የአሸባሪው ሸኔ ቡድንና ግብረ አበሮቹ በሕገወጥ መንገድ እያደረጉት ያለው ተግባር የሀገርን የልማት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ያለመ ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ብሔራዊ ባንክ የዲጂታል ክፍያ በኪውአር (QR) ኮድ እንዲሆን ትዕዛዝ መስጠቱን ገለጸ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለሁሉም የክፍያ አገልግሎት ሰጪዎች የዲጂታል ክፍያ በQR ኮድ ከሕዳር 22 ቀን 2017 ጀምሮ ተግባራዊ እንደያደርጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አዲሱ መመሪያ ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ ነጻ የሆነውን የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለማጎልበት እየተሰራ ያለውን ሥራ ለማጠናከር እንደሚያግዝ እና የዲጂታል ግብይትን እየለመደ ያለውን ማህበረሰብ በይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ይህ ኢት ኪውአር ኮድ (EthQR Code) የሚል ሥያሜ የሚኖረው አሠራር ዓለምአቀፍ የአሠራር ልምዶችን መሠረት ያደረገ፣ የክፍያም ሆነ የግብይት ተዋናያንን ሙሉ መረጃ የሚይዝ ነገር ግን ከተወሰኑ አስፈላጊ መረጃዎች በቀር ሌሎቹን በምሥጢር የሚጠብቅ ሥርዓት መሆኑን ባንኩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ይህም የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትና ግብይት የጥሬ ገንዘብን ዝውውር የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ፣ ሕብረተሰቡ ለሥርቆት፣ በእጁ ያለው ገንዘቡም ለእርጅና እንዳይጋለጥ፤ ከባንክ ውጭ የሚዘዋወር የገንዘብ መጠን እንዲቀንስ፣ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ገንዘቡን ለማሳተም የሚወጣ ወጪን እንዳይጨምር ለማድረግ እንደሚረዳ ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ዓመት "በሲስተም መበላሸት" ከተወሰደበት ገንዘብ ያልተመለሰው 217 ሺሕ ብር ብቻ መሆኑን አስታወቀ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳይበር ድህንነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሳይበር ድህንነት ቀን እያከበረ ይገኛል።
በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፤ ባለፈው ዓመት በራሳችን ስህተት በተፈጠረው የሲስተም ችግር ምክንያት ከተወሰደው ገንዘብ ሁሉም ተመልሶ የቀረው 217 ሺሕ ብር ብቻ ነው ብለዋል።
"የሳይበር አለም አስፈሪ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ሥራ ይፈልጋል ብለዋል።
"ባለፈው ዓመት የተፈጠረው ችግር በፍጥነት አጥፍፊዎች መታወቃቸው ነው እንጂ፤ ችግሩ ከውጪ የመጣና መቆጣጠር የማንችለው ቢሆን ጥፋቱ ከፍተኛ ይሆን ነበር" ብለዋል።
ባንኩ ባለፈው ዓመት መጋቢት 6 ለሊት የሲስተም ችግር በገጠመው ወቅት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር (40 ሚሊዮን ዶላር) እንደተወሰደበት ይታወሳል።
10 ሺሕ የሚሆኑ ግለሰቦች የገንዘብ ዝውውር ማድረጋቸውም ተገልጾ ነበር።
በአቤል ደጀኔ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በየሳምንቱ በአማካይ ከ70 ሺሕ በላይ የወባ ሪፖርቶች እንደሚደርሰው የአማራ ክልል ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአማራ ክልልን ከ80 በመቶ በላይ የቆዳ ስፋት በሚሸፍኑት የምዕራብ አማራ፣ ጎንደር፣ ጎጃም እንዲሁም በምስራቅ አማራ ሰሜን ወሎ አከባቢዎች ከመስከረም ወር መግቢያ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የወባ ወረርሽኝ መስፋፋቱ ተገልጿል፡፡
በክልሉ በ40 ወረዳዎች በየሳምንቱ የሚደረገው የወባ ምርመራ ሪፖርት እንደሚደርሳቸው የገለጹት፤ የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ናቸው፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በየሳምንቱ በአማካይ ከ70 ሺሕ በላይ የወባ ሪፖርቶች ለኢንስቲትዩቱ እንደሚደርሰው ተናግረዋል፡፡
ከወባ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የመድኃኒት እጥረት መኖሩን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጉዳዩን በተደጋጋሚ ለጤና ሚኒስቴር ማቅረባቸውን ነግረውናል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሳምንት በቂ የወባ በሽታ መድኃኒት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን መግለጹ አይዘነጋም።
የወባ ወረርሽኝ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በስፋት እየተስተዋል የሚገኝ ሲሆን፤በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማን ጨምሮ በሰባት ወረዳዎች እንዲሆም በወላይታና በሌሎች ከተሞች እና እካባቢዎች በአሳሳቢ ደረጃ እየተከሰተ መሆኑ እየተዘገበ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት አዲስ ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ከታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ፤ ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 1 ሺሕ 157 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።
በሪፖርቱ ወባ አሁንም አሳሳቢ የጤና ስጋት መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ 75 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ መሬት እና 69 በመቶ የሚሆነው በነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ በተለይም ሕጻናት ለከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡
በፅዮን ይልማ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ወደ ሌጎስ እንደሚያደርግ ተገለጸ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ወደ ናይጀሪያ ሌጎስ እንደሚያደርግ አየር መንገዱ አስታውቋል።
ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን፤ ከፈረንሳይ ቱሊስ ተነስቶ ከትናንት በስቲያ ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።
አውሮፕላኑ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ አቪዬሽን ሳንስ ፍሮንቲርስ ከኤርባስ ኩባንያ ጋር በመተባበር ለኢቲ ፋውንዴሽን ያበረከቱትን ከ100 ሺሕ ዩሮ በላይ የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁሶች ይዞ መግባቱም ይታወሳል።
አሁን ደግሞ የመጀመሪያ በረራውን ከአዲስ አበባ ወደ ናይጀሪያ ሌጎስ እንደሚያደርግ ተነግሯል።
ይህ ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ለንደን፣ ፓሪስ እና ፍራንክፈርትን ጨምሮ፤ ወደ ሌሎችም ቁልፍ መዳረሻዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ እንደሚያስችለው ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት የ ኤ350 ቤተሰብ የሆኑ 21 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው።
በሚቀጥሉት ዓመታት 11 ኤ350-900 እና ሦስት ተጨማሪ ኤ350-1000 አውሮፕላኖችን ጨምሮ 14 ተጨማሪ ኤ350 አውሮፕላኖችን የአየር መንገዱ ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል።
የኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን በአጠቃላይ 395 መንገደኞችን (46 ቢዝነስ እና 349 የኢኮኖሚ ደረጃ መቀመጫዎች) ማስተናገድ የሚችል ነው።
"ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ" የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አውሮፕላን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመንገደኞችን የማጓጓዝ አቅም ያሳድጋል ተብሎለታል።
A350 በዓለም ላይ በጣም ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የሆነ ባለ ግዙፍ አካል አውሮፕላን ሲሆን፤ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እና የኤሮዳይናሚክስን ውጤቶችን አካቷል።
ከቀድሞ የአውሮፕላን ስሪቶች ጋር ሲነጻጸር በበረራ ወቅት የሚፈጥረው ድምጽ 50 በመቶ ያነሰ መሆኑም ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ የመማሪያ ክፍሎች በከፊል ከጥቅም ዉጭ ሆነዋል ተባለ
ጥቅምት 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በወረዳው በሚገኙ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ተፈጥሯ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አደምበላህ ሀመዱ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በወረዳው በተደጋጋሚ እየተከሰተ በሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ በስፍራው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት መማሪያ ክፍል ውጭ ትምርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
"በአካባቢው እየተከሰተ የሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ ከዚህ ቀደም በተሰነጠቀ ቦታ ላይ በተመሳሳይ አደጋው የሚከሰትበት ሁኔታ በመኖሩ ስጋት ፈጥሯል" ሲሉም አክለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በወረዳው ሳቡሬ ቀበሌ ኡንጋይቱ አንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት በመሬት ማንቀጥቀጡ ምክንያት የት/ቤቱ ጣሪያ፣ ግድግዳ እና ወለል በመሰነጣጠቁ በመምህራን እና ተማሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል መምህራን ተማሪዎቹ በሜዳው ላይ ለማስተማር መገደዱን አስታውቆ ነበር።
በክልሉ እየተከሰተ ያለው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የመሬት መሰጠንቅ፣ መኖሪያ ቤቶች ላይ ቀለል ያለ መፍረስና መሰንጠቅ እንዲሁም በእንስሳቶች ከፍተኛ ድንጋጤ እና መጠነኛ ጉዳት ማስከተሉ የተነገረ ሲሆን፣ የመሬት መንቀጥቀጡ ያስከተላቸው ተደጋጋሚ ንዝረቶች አዲስ አበባ ድረስ መሰማታቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህም የመሬት መጥቀጥቀጥ የሬክታል ስኬል መጠን ከ4 ነጥብ 5 እስከ 4 አጥብ 9 እየጨመረ የሚገኝበት ሁኔታ እንዳለ መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ዙምባቡዌ የሀገሪቱ የፖሊስ ሰራዊት አባላት የእጅ ስልክ እንዳይጠቀሙ አገደች
ጥቅምት 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ዙምባቡዌ የሀገሪቱ የፖሊስ ሰራዊት አባላት በሥራ ላይ እያሉ ሞባይል ወይም የእጅ ስልክ እንዳይጠቀሙ ስትል እግድ አዉጥታለች።
ሀገሪቱ በሥራ ስዓት የትኛዉም የፖሊስ ሰራዊት የሞባይል ስልክ መጠቀም በሕግ እንደሚያስቀጣ አስጠንቅቃለች።
በዚህም መሰረት በሀገሪቱ በሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች “ማንኛውም አባል በሥራ ላይ እያለ ሞባይል እንዲይዝ አይፈቀድለትም። ሞባይል ስልኮች በእረፍት እና በምሳ ሰአት ብቻ መጠቀም አለባቸው።" የሚል ማሳሰቢያ መሰራጨቱ ተነግሯል፡፡
ይህንን ዉሳኔ ለመወሰን የተገደደችዉ ዚምባቡዌ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ ነዉ ሲል የሀገሪቱ መንግሥት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል።
በቅርቡ የዚምባብዌ ሁለት የትራፊክ መኮንኖች ከሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎች ጉቦ ሲቀበሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር ነበር፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ዶናልድ ትራምፕ 47ተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ እየተዘገበ ይገኛል
ጥቅምት 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በከባድ ፉክክር በታየበት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን ወደ አሸናፊነት እየተቃረቡ መሆኑ እየተዘገበ ይገኛል፡፡
'ፎክስ ኒውስ' አሁን ላይ ባወጣው አጠቃላ ትንበያ ዶናልድ ትራምፕ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ ጠቁሟል።
በዚህ ውጤቱ በፍጥነት መቀያየር በታየበት ፉክክር አሁን ላይ ለማሸነፍ ከሚያስፈለገው አጠቃላይ 270 ድምጽ ውስጥ ዶናልድ ትራምፕ 267 ድምጽ አግኝተው ፉክክሩን ለማሸነፍ ሦስት ድምጾች ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡ ሃሪስ ደግሞ በ216 ድምጽ እየተከተሉ ይገኛል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን የፉክክሩን አሸናፊ ከሚወስኑ ሰባት ግዛቶች መካከል ሰሜን ካሮላይና እና ጆርጂያ ላይ ያሸነፉ ሲሆን፤ በተቀሩት አምስቱም ግዛቶች ላይም በመምራት ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ አምስት ግዛቶች አሪዞና፣ ኔቫዳ፣ ሚሺጋን፣ ፔንሲልቫኒያ እና ዊስከንሰን ሲሆኑ፤ በእነዚህ ግዛቶች ላም ትራምፕ የበላይነቱን በመቆጣጠር ላይ ይገኛሉ፡፡
በርካታ መገናኛ ብዙሃን እና የምርጫ ሂደት ተንታኞች የአሸናፊነቱን ግምት ለሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ሰጥተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሩብ ዓመቱ ከ4 መቶ በላይ አቤቱታዎች ቀርበው 24 መዝገቦች እልባት ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 ዓ.ም ሩብ ዓመት 413 አቤቱታዎች ቀርበው 24 መዝገቦች እልባት ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም የህዝብ ግንኙነትና ኮምንኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንለይ ወርቄ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ የቀረቡ ቅሬታዎች ደግሞ በብዛት ከመሬት ይዞታና ከትምህርት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች መሆናቸውን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
ከቀረቡት አጠቃላይ አቤቱታዎች መካከል 172 የሚደርሱ አቤቱታዎች ደረጃቸውን ጠብቀው የቀረቡ ሲሆን፤ ቅሬታዎቹም በምርመራ ሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ 116ቱ አቤቱታዎች ደረጃውን ጠብቀው ያልቀረቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከቀረቡ አቤቱታዎች መካከል 125 መዝገቦች ተቋሙ በተሰጠው ስልጣንና መመሪያ መሰረት ተፈጻሚ ሊያደርጋቸው የማይችሉ ወይንም ተቋሙን የማይመለከቱ አቤቱታዎች መመሆናቸውን አቶ አንለይ ወርቄ ገልጸዋል፡፡
በምርመራ ላይ ያሉ መዝገቦችን በተመለከተም ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የምርመራ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርጉም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በአለምነው ሹሙ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ!
የመዋቅር ጥያቄ ባለመመለሱ ለግጭት መንስኤ መሆኑ ተገለጸ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ፤ የዘይሴ ቀበሌ ማህበረሰብ ለረጅም ዓመት የቆየ የመዋቅርጥያቄ እንዳለው፤ የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ እሳቱ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
የማህበረሰብን የመዋቅር ጥያቄ ለመመለስ በዞንም ይሁን በክልል ደረጃ ጥናት የተደረገ ቢሆንም፤ እስካሁን ጥያቄው ምላስ አለማግኘቱን አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡ ይህም በአካባቢው ለሚታየው ግጭት መንስኤ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኃላ ጥያቄያችንን ይመልሳል የሚል ተስፋ ቢኖርም፤ በአካባቢው ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ ይልቅ ኢዜማ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱን እና መመረጡን አስታውሰዋል፡፡
"በዚህም ምክንያት 'ኢዜማን ትደግፋላችሁ' በሚል በመንግሥት በኩል የዞንም ሆነ የልዩ ወረዳ እውቅና አልተሰጠውም" ሲሉ አስተዳዳሪው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"ጥያቄያችንን ለዞኑም ሆነ ለክልሉ መንግሥት ብናቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
"የማህበረሰቡ ጥያቄ ከብልጽግናም ሆነ ከኢዜማ ጋርም የሚያገናኛው ነገር የለም" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ በአካባቢው መንገድ፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት በመንግሥት በጀት እየተሰሩ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመዋቅር ጥያቄ አለመመለሱ የእርስ በእርስ ግጭቶች መንስኤ መሆኑን የገለጹት አቶ እንግዳ ፤ "በዚህም ምክንያት የጸጥታ ሀይሎችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች እንዲሞቱና ሌሎች ጫካ እንዲገቡ ሆናል" ብለዋል፡፡
"በክልልም ሆነ በፌደራል መንግሥት መቀመጫ የያዙት የአካባቢው የህዝብ ተወካይዎች በአግባቡ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፡፡ የማህበረሰቡን ጥያቄ ከማንሳት ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ያስቀደሙ ሆነዋል" ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
መንግሥት ይሄን የመዋቅር ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል የሚል እምነት እና ተስፋ እንዳላቸውም አስተዳዳሪው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በፍቅርተ ቢተው
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ!
በዛሬው ዕለት በሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ አንድ እናት ከስድስት ወር ልጇ ጋር ሕይወቷ ማለፉ ተሰማ
👉በእሳት አደጋዉ ስድስት የንግድ ሱቆች ተቃጥለዋል ተብሏል
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ ዛሬ ጥቅምት 26 ቀን 2017 በመስሪያና መሸጫ ሼድ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ አንድ እናት ከስድስት ወር ልጇ ጋር ሕይወቷ ማለፉ ተሰምቷል፡፡
ከንግድ ሱቆቹ መካከል በአንደኛዉ ነዳጅ በፕላስቲክ ጠርሙስ በችርቻሮ የሚሸጥበት ሱቅ በመሆኑ ለሽያጭ የተዘጋጀዉ ነዳጅ ለቃጠሎው መከሰትና መባባስ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
ከስድስት ወር ልጇ ጋር ሕይወቷ ያለፈችዉ እናት በእሳት አደጋዉ ከተቃጠሉት የንግድ ሱቆች ዉስጥ በአንደኛዉ ሱቅ የንግድ ሥራ ላይ የነበረች መሆኑ ታውቋል።
በተጨማሪም በእሳት አደጋዉ በሼድ ዉስጥ ካሉ ሱቆች መካከል ስድስት የንግድ ሱቆች መቃጠላቸው ተገልጿል።
የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር ሦስት የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ፣ ሁለት አምቡላንሶች ከሰላሳ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር የተሰማሩ ሲሆን፤ የእሳት አደጋዉ ወደሌሎች ንግድ ሱቆች ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለሸገር ሬዲዮ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ነዳጅ መከማቸትም ሆነ መሸጥ ያለበት በተፈቀደለትና የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ባሟሉ የነዳጅ መሸጫ ጣቢያዎች ዉስጥ ብቻ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ በተለያዩ የንግድ ሱቆች ዉስጥ ነዳጅ ማከማቸትም ሆነ መሸጥ መሰል አደጋዎችን የሚያስከትል በመሆኑ የንግድ ፈቃድ የሚሰጡ አካላትም ተገቢዉን ቁጥጥር ማድረግ እንደሚኖርባቸው አሳስቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ!
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሲደረግ በቆየው የቡና ዋጋ ገደብ አሰራር ላይ ማሻሻያ መደረጉን ተነገረ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ገበያ መር እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ፤ የግብይት ሰርአቱ ላይ ማሻሻያ መደረጉን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታውቋል።
ምርት ገበያው፤ ማሻሻያው ባለፉት ዓመታት ተዛብቶ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ስርአት ለማስተካከል የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን ገልጿል።
መንግሥት ያደረገው የኢኮኖሚ ሪፎርም ተከትሎ ቡና አምራቾች ከግብይት ስርአቱ ማሻሻያ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ማሻሻያ መደረጉ ነው ያስታወቀው።
በዚህ መሰረትም ባለልዩ ጣእም ቡና በኒዎርክ የቡና ገበያ ዕለታዊ ዋጋ ማሳወቂያ ሰንጠረዥ መሠረት እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፤ ለንግድ የሚውለው የቡና ምርት ደግሞ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በሚመራው የገበያ ስርአት መሠረት ግብይቱ እንዲካሄድ ተብሏል።
ቀደም ሲል የቡና መሸጫና መግዣ በምርት ገበያ በማነፃፀርያ የግብይት ሰንጠረዥ ስርአት ሲገበያይ የቆየ ሲሆን፤ በተሻሻለው መመርያ ባለ ልዮ ጣእም ቡና በኒዎርክ ገበያ ባለው ዋጋ እንዲቀርብ መወሰኑን አሐዱ ከባለስልጣኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎችና በተቀመጠው መመርያ መሰረት ግብይት እንዲያደርጉ መወሰኑንም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታውቋል።
ማሻሻያው መንግሥት የቡና ገበያ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ተነግሯል።
በአማኑዔል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚፈፅሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሽግግር ፍትሁ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም ከሰሜኑ ከጦርነት በኃላ እስካሁን ያልተፈቱ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግሮች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተደጋጋሚ ሪፖርቶችን ሲያወጣ ይስተዋላል።
"ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ስምምነቶችን የፈረመች እንዲሁም ሕጎችን ያወጣች ቢሆንም የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ከማድረግ አንጻር እንዴት ትገመገማለች?" ሲል አሐዱ ጠይቋል።
በአንዳንድ የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በነበረዉ ግጭት በርካታ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸዉን በተለይም የዜጎች በሕይወት የመኖር መብታቸዉ ጥያቄ ዉስጥ መግባቱን በተደረገ ክትትልል እና ሪፖርቶች ማወቅ መቻሉን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ ገልጸዋል።
"ለእነዚህ ሰብዓዊ መብቶች እና ድንጋጌዎች መከበር የሽግግር ፍትህ ሁነኛ አማራጭ ነዉ" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
መንግሥት በተለይም በጦርነት የደረሱ ጉዳቶችን ከመመርመር አንጻር እና የሰብዓዊ ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር እና ከመካስ አኳያ አሁንም መሰራት እንዳለበትም አመላክተዋል።
አክለዉም፤ እነዚህን አለምአቀፍ ስምምነቶች ከሀገር ዉስጥ ህጎች ጋር አጣጥሞ ከማቅረብ አንጻር ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ነዉ የገለጹት።
በፅዮን ይልማ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከፍለው መማር የማይችሉ 500 ወጣቶች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስልጠና በነጻ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ ተነገረ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ከክራፍት ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ከፍለው መማር ለማይችሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሕጻናት የነጻ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ይህ የተባለው ክራፍት ፋውንዴሽን በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ያሰለጠናቸውን 80 ወጣቶች ባስመረቀበት ወቅት ነው፡፡
የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈጻሚ አንተነህ ክፍሌ እንደተናገሩት፤ የአንድ ዓመት ስልጠናውን ወስደው የተመረቁት ተማሪዎች በስልጠና ላይ ከሚገኙት 500 ተማሪዎች መካከል መውሰድ የሚገባቸውን ትምህርት በብቃት ያጠናቀቁ ናቸው፡፡
ሥራ አስፈጻሚው፤ ድርጅቱ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሕጻናትን ለማገዝ እንደተቋቋመ እና ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ጋር በመተባበር ስልጠናውን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አንስተው፤ ሚንስትር መስሪያቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተማዎች የሚኖሩና ከፍለው የመማር አቅም የሌላቸውን ለይቶ እንደሚልክለት ተናግረዋል፡፡
መቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ያደረገው ክራፍት ፋውንዴሽን ኡጋንዳ፣ ናይሮቢ፣ ህንድ ለሚገኙ ወጣቶች እና ሴቶች ነጻ የትምህርት እድል በማመቻቸት የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ስልጠና በመስጠት ይታወቃል፡፡
በአለምነው ሹሙ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵውያን መብት ጠየቀ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ የሚመለከታቸው አካላት መስራት እንዳለባቸው የገለጹት፤ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ግሎባል ለኢትዮጵያውያን መብት የተባለው ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ መሱድ ገበየሁ ናቸው።
አቶ መሱድ ይህንን ያሉት ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብት በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ያሰባሰበውን 4 ሚሊየን 640 ሺሕ ብር ባስረከቡበት መርሃ ግብር ላይ ነው ።
ግሎባል አሊያንስ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ለትምህርት ቤት ግንባታና ቁሳቁስ ማሟያነት የሚውል ለእያንዳንዳቸው 2 ሚሊየን 320 ሺሕ ብር ለአማራ ልማት ማህበር እና ለአፋር ልማት ማህበር ተወካዮች አስረክቧል።
ከዚህ በፊት ድርጅቱ ባደረገው ድጋፍ በአፋር ክልል ሎጊያ ከተማ ላይ ትምህርት ቤት መገንባቱንና በአማራ ክልል ሀይቅ ቁጥር 1 ትምህርት ቤት ላይ ደግሞ የግብዓት ማሟላት ሥራ ማከናወኑን የገለፁ ሲሆን፤ "ይህን መሰሉ ጥረት ትርጉም እንዲኖረው ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል" ብለዋል።
"የገንዘብ ድጋፉም ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እና እነዚህን ትምህርት ቤቶች በሙሉ ቁመና ወደ መማር ማስተማር እንዲመለሱ ለማድረግ የተሰጠ ነው" ያሉት ተወካዩ፤ "እኛ ትምህርት ቤት እየገነባን መልሶ ከፈረሰና ካምፕ ከሆነ ጥረታችን ትርጉም አልባ ይሆናል" ብለዋል፡፡
ግሎባል አሊያንስ ባለፋት ስድስት ዓመታት ብቻ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ባለፉት ሦስት ወራት 507 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች አካላት መሰረቃቸው ተገለጸ
👉የሦስት ወራቱ ስርቆት በአምስት ዓመታት ውስጥ ከተፈፀመው ጋር እጅግ ተቀራራቢ ነው ተብሏል
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ባለፉት ሦስት ወራት 507 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አካላት መሰረቃቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ አንድ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ አስታውቋል።
የተቋሙ እና የዞኑ አመራሮች ጋር በመሰረተ ልማት ላይ ስለሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎች በተወያዩበት መድረክ ላይ የሪጅኑ የቴክኒክ ባለሙያ አቶ በሱፈቃድ ባዩ እንደገለጹት፤ በሪጅኑ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ1 ሺሕ 3 መቶ በላይ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አካላት ላይ የስርቆት ወንጀል ተፈፅሟል።
ከዚህ ውስጥ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ቦርደዴ፣ መኤሶ፣ ቡሲን አርቤ እና ኪቶን ካራ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች 507 የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አካላት ተሰርቀዋል።
ጉዳት የደረሰባቸውን የምሰሶ አካላት ዳግም ለመጠገን ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።
ከ2011 እስከ 2016 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚያልፉ 119 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ምሰሶዎች ላይ 744 ብረቶች ለስርቆት እንደተዳረጉ የጠቀሱት ባለሙያው፤ ስርቆት የተፈፀመባቸውን የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውሰዋል።
እንደ አቶ በሱፈቃድ ገለጻ፤ በዞኑ እና በከተማ አስተዳደሮቹ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የተፈፀመው የስርቆት ወንጀል በአምስት ዓመታት ውስጥ ከተፈፀመው ዝርፊያ ጋር እጅግ ተቀራራቢ ነው።
"ይህም በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢነቱ እየጨመረ ለመምጣቱ ማሳያ ነው" ብለዋል።
በአካባቢው በተደራጀ መልኩ ስርቆት የሚፈፀም መሆኑ፣ የወሰን ማስከበር ጉዳይ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ እና የሥራ ትብብርን ከጥቅም ጋር የማያያዝ እንዲሁም ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት አፋጣኝ ጥቆማ አለመስጠቱ ለስርቆቱ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ባለሙያው ማብራራታቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሰብአዊ ድጋፍ እጥረት ምክንያት አረጋዊያን ለረሀብ ተዳርገዋል ተባለ
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅ እና በሰብአዊ ድጋፍ እጥረት ምክንያት አረጋዊያን ለረሃብ መጋለጣቸውን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ እንዳለው፤ ችግሩ በአረጋዊያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ ማዕከላት ውስጥም መታየት ጀምሯል።
በአዕምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ ማዕከላት ውስጥ በሚገኙ ሴት የአዕምሮ ሕሙማን ላይ ጾታዊ ጥቃት ስለመኖሩም መግለጫው አንስቷል።
በሚጣሉ የሰዓት እላፊ እና የእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት በአነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ሥራ ዘርፍ የሚተዳደሩ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን የችግሩ ሰለባ መሆናቸውንም አብራርቷል።
ኢሰመኮ በመግለጫው "አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች አመቺ እና ተደራሽ ምትክ ቦታዎች ባለመሰጠታቸው አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ለከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ተጋልጠዋል" ብሏል።
የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ሰብአዊ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ ለማክበር፣ ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት ያስችላሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦችም በመግለጫው አካቷል።
በምክረ ሐሳቡም የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እስከ አሁን በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የአካል ጉዳተኞች መብቶች አዋጅ ግልጽና አሳታፊ በሆነ መንገድ ፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ ሊገባ የሚችልበትን ሁኔታ እንዲያመቻች የጠየቀ ሲሆን፤ ሌሎች መስተካከል እና መሻሻል አለባቸው ያላቸውን ጉዳዮች አንስቷል።
በወልደሀዋሪያት ዘነበ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
#ADVERTISMENT
#AhaduBank
🔊ለአሐዱ ባንክ አ.ማ. ባለአክሲዮኖች በሙሉ
የባለአክሲዮኖች 3ተኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሚኒሊየም አዳራሽ ይካሄዳል።
በመሆኑም የባንኩ ባለአክሲዮኖች ወይም ህጋዊ ወኪሎቻቸው በተጠቀሰው ቀን፣ ሰዓት እና ቦታ በጉባዔው ላይ እንዲገኙ የዳይሬክተሮች ቦርድ በአክብሮት ጥሪውን ያስተላልፋል።
አሐዱ፡ባንክ
ከብዙዎች ለብዙዎች
የአሐዱ፡ባንክ ማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ
👉https://linktr.ee/Ahadu_Bank
#አሐዱ_ለዛና_ቁምነገር
"ባንዲራችን መሃሙድ አህመድ" በአለምነህ ዋሴ
ሙሉ ጥንቅሩን ለመከታተል ከሥር ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ!
👇
https://youtu.be/uClzQ0nyzvU?si=9mrfQuNs9uYWDG2v
ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ገለጹ
👉ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድን ለትራምፕ "የእንኳን ደስ አሎት!" መልዕክት አስተላልፈዋል
ጥቅምት 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሪፐብሊካኑ እጩ ዶናልድ ትራምፕ የ2024ቱን የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን በፍሎሪዳ በተካሄደ መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉበት ንግግር " አስደናቂ ድል አስመዝግበናል" ያሉ ሲሆን፤ "ይህ የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን ይሆናል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ አስገራሚ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ታይቶ አይታወቅም በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አስደናቂ ወዳጆች አሉን። ይህን እንቅስቃሴ ማንም ከዚህ በፊት አይቶት አያውቅም።" ሲሉም ለደጋፊዎቻቸው ገልጸዋል፡፡
አክለውም፤ "በእውነትም ይሄ እኔ እንደማምነው የምንጊዜውም ታላቁ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው።" ያሉ ሲሆን፤ "ይህ ለአሜሪካ ህዝብ ታላቅ ድል ነው፤ አሜሪካን እንደገና ታላቅ ለማድረግ ያስችለናል" ብለዋል፡፡
"አሜሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ስልጣን ሰጥታናለች" ያሉት ዶናልድ ትራምፕ፤ "የምታገለው ለእናንተ ነው" ሲሉም ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል፡፡
ዶናንድ ትራምፕ አስገራሚ ፉክክር በታየበት በ2024ቱ የአሜሪካ ምርጫ ካማላ ሀሪስን አሸንፈው ዳግመኛ የልዕለ ሀያሏ ሀገር አሜሪካ 47ተኛው ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለ47ተኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናንድ ትራምፕ "የእንኳን ደስ አሎት!" መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የአይን ብሌን ልገሳ ከሚያደርጉ ግለሰቦች የጉበት ቫይረስ እየተገኘ መሆኑ ተገለጸ
ጥቅምት 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአይን ብሌን ከሚለግሱ ዜጎች አምስት ተላላፊ በሽታዎች ምርመራ እንደሚከናወን እና የጉበት ቫይረስ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በዚህም የኤች አይ ቪ፣ የጉበት ቫይረስ በሽታ እና ቂጥኝ እንዲሁም ኮቪድ 19 ጨምሮ ምርመራ እንደሚደረግ የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ የአይን ብሌን ከሚለግሱ ዜጎች የአይን ብሌን ምርመራ በሚከናወንበት ወቅት የጉበት ቫይረስ በሽታ ወይም ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ እንደሚገኝ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ተዛማች እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግበታል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከ120 በላይ የሚሆኑ ዜጎች የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ ለማከናወን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ እንዲያከናውኑ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከሕክምና ተቋማት እንደሚላክላቸው የገለጹት ምክትል ዋና ዳሬክተሩ፤ ምን አልባት ከ120 ሊጨምር የሚችልበት እድል ስለመኖሩም ተናግረዋል፡፡
77 ለሚሆኑ ሰዎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ለማከናወን ታቅዶ እንደነበር ያነሱም ሲሆን፤ 81 ለሚሆኑ ዜጎች ከህልፈተ ሕይወት በኋላ የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ መከናወን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አክለውም፤ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ የአይን ብሌን ለመለገስ ቃል የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ዝቅተኛ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ "ከ150 ዜጎች 60 የሚሆኑት ብቻ የአይን ብሌን ከእልፈተ ህይወት በኋላ ልገሳ ለማከናወን ቃል የገቡ ናቸው" ብለዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ዶናልድ ትራምፕ በጠባብ ልዩነት እየመሩ ነው
ጥቅምት 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተጠባቂው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ዲሞክራቷን ካማላ ሀሪስ በጠባብ ልዩነት በመምራት ላይ ይገኛሉ።
የፕሬዝዳንታዊ ውድድሩ በሁሉም 50 ግዛቶች እና በኮሎምቢያ ዲስትሪክት ውስጥ የሚገኙ መራጮች ድምጽ እየሰጡበት ይገኛሉ።
በዚህም ዶናልድ ትራምፕ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ተፎካካሪያቸውን በሰፊ ልዩነት ሲመሩ የቆዩ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ካማላ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት አጥበውታል።
በዚህም ሃሪስ ከትራምፕ ጋር የነበራቸውን ልዩነት በማጥበብ በአሁኑ ወቅት፤ 210 የመራጮች ድምጽ ሲያገኙ ትራምፕ 247 ድምፅ መሰብሰባቸውን ቅድመ መረጃዎች አሳይተዋል።
በተጨማሪም የዶላንድ ትራምፑ ፓርቲ ሪፐብሊካኖች የዩኤስ ሴኔት አብላጫ ድምፅን አሸንፈው፤ ከ4 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ምክር ቤቱን መቆጣጠራቸውን ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
47ተኛውን ፕሬዚዳንቷን በምትመርጠው አሜሪካ አሁንም የሁለቱ እጩዎች ፉክክር አጓጊ ሆኖ እንደቀጠለ ሲሆን፤ አጠቃላይ ውጤት ለማወቅ "ስዊንግ ስቴት" የሚባሉትን 7 ግዛቶች የምርጫ ውጤት መጠበቅ ግድ ይላል።
በአጠቃላይ 270 የወኪል መራጮችን ድምጽ ያገኘ እጩ፤ በቀጣይ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ሀገሪቷን ይመራል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
#አሐዱ_ልዩ_ቃለ_ምልልስ
ተጠባቂውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አስመልክቶ ከአሜሪካ አለምዓቀፍ ሚዲያ ተቋም የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ዳይሬክተር ጋር የተደረገ ቆይታ፡፡
Exclusive interview with Joan Mower፣ Director, Office of Business Development at United States Agency for Global Media/USAGM/
ዳይሬክተሯ ከአሐዱ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ለመከታተል ከስር ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/GodEen_5GmM?si=idvYY9MRnDiJa_wN
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የብሪክስ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር መስራች አባል ሆነ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የብሪክስ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር መስራች አባል መሆኑን አስታውቋል።
ዩኒቨርሲቲው ሩሲያ፣ ህንድና ብራዚልን ጨምሮ ከብሪክስ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን በጣምራ የብሪክስ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ማኅበርን በመመስረት የመጀመሪያው የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ዩኒቨርስቲ መሆኑን ገልጿል።
አራቱ የብሪክስ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች የመሰረቱት ማህበር በትምህርት፣ በዲፕሎማሲ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በፈጠራ ሥራ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
ዩኒቨርስቲው በአዲሱ የራስ-ገዝ ስትራቴጂክ እቅድ መሰረት በአጋርነትና ዓለማቀፋዊነትን ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ!
#አሐዱ_አሳሩ_በዛብህ
አሳሩ በዛብህ በሳምንቱ አሳሰበኝ ያለውን ጉዳይ በብዕሩ ከትቦ ለወዳጁ ምክረ ሰናይ ልኮለታል፡፡ አሳሩን ያሳሰበው ጉዳይ ምን ይሆን?
ሙሉ ጥንቅሩን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/ARjlN73uLsA?si=AUdsPoypyoNGLQaZ
#UPDATE
በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነው ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ዛሬ አዲስ አበባ ገባ
ጥቅምት 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና A 350-1000 "Ethiopia land of origins" የሚል ስያሜ የተሰጠው የመንገደኞች አውሮፕላን በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብቷል።
አውሮፕላኑ አቪዬሽን ሳንስ ፍሮንቲርስ ከኤርባስ ኩባንያ ጋር በመተባበር ለኢቲ ፋውንዴሽን ያበረከቱትን ከ100,000 ዩሮ በላይ የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁሶች ያጓጓዘ መሆኑን የአየር መንገዱ መረጃ ያመለክታል፡፡
አዲስ አበባ ቦሌ አለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ ሚኒስተሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ደማቅ የአቀባበል ሥነ-ስርዓት ተደርጎለታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን በፈረንሳይ ቱሉዝ በተካሄደ ሥነ-ስርዓት ከኤርባስ ኩባንያ መረከቡ ይታወቃል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ