የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ ይከበራል
ጥቅምት 4/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ተከብሮ ይውላል፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ቀን የጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሰኞ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡
በዚህም መሠረት የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ በዛሬው ዕለት ተከብሮ ይውላል።
ቀኑ በፌደራል የመንግሥት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢምባሲዎችና ሚሲዮኖች ይከበራል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በመዲናዋ 453 በላይ ምግብ ነክ አምራች ተቋማት የጥራት መለኪያውን ባለሟሟላታቸዉ ዕድሳት አለማድረጋቸው ተገለጸ
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሩብ ዓመቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ 2 ሺሕ 200 ምግብ ነክ አምራች ተቋማት ዕድሳት ያደርጋሉ በሚል እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ከነዚህ ዉስጥ 453 በላይ የሚሆኑት የፍቃድ ዕድሳት አለማድረጋቸውን የከተማ አስተዳደሩ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ብቃት ማረጋጋጥ ዳይሬክተር ቤዛዊት ግርማ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ እንደ ተቋም በሩብ ዓመቱ ከ2 ሺሕ 200 በላይ በከተማዋ የሚገኙ ተቋማቶች ዕድሳት ያደርጋሉ ተብሎ በእቅድ ተይዞ ነበር።
ነገር ግን ከ1 ሺሕ 7 መቶ በላይ ተቋማት እድሳት እንዳደረጉና ቀሪ 453 በላይ ተቋማት ደግሞ ከገበያው በመውጣት፣ የጥራት መለኪያውን ባለሟሟላትና በተለያዩ ሌሎች ምክንያቶች ዕድሳት አለማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ከመስከረም 30 በኋላ እስከ ታህሳስ 30 ድረስ በቅጣት ነባሮችና አዲስ ተቋማት ፍቃድ ማግኘት እና ማደስ እንደሚችሉም ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።
አያይዝውም በዘርፉ የሚስተዋሉ መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮች ተለይተው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያያት በቅንጅት ችግሩን ለመቅረፍ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ተቋማቱ በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት የፍቃድ ዕድሳት እንዲያደርጉ ወ/ሮ ቤዛዊት ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ "በተጠቀሰው የቅጣት እድሳት ጊዜ ተጠቅመው ዕድሳት የማያከናውኑ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቱ እንደተሰረዘ ይቆጠራል" ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በወልደሀዋርያት ዘነበ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በኢትዮጵያ የአእምሮ ሕክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት ቁጥር 270 መድረሱ ተገለጸ
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአለም አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ጤና ቀን በዚህ ሳምንት የተከበረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም "በሥራ ቦታ ለአዕምሮ ጤና ቅድሚያ የሚሰጥበት ጊዜ ነው" በሚል መሪ ቃል ታስቦ ውሏል።
በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአእምሮ ጤና ባለሙያ አቶ ጀማል ተሾመ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ270 በላይ የጤና ተቋማት የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
በኢትዮጽያ የዜጎች ከፍተኛ የጤና ጠንቅ ከሆኑ መካከል የአእምሮ ጤና እክል ዋንኛው መሆኑን ያነሱት ባለሙያው፤ ይህንን ለመቀነስ ለሕክምና ባለሙያዎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአእምሮ ሕመም የሚውሉ መድሃኒቶች እጥረት መኖሩና የተለያዩ አይነቶች መድሃኒቶች መለዋወጥ በታካማዊች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ለአእምሮ ጤና እና ሕመም ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ የገልጹት፤ የአዕምሮ ጤና ባለሙያው አቶ ጀማል ማህበረሰብ ተኮር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
አክለውም ስለ አእምሮ ጤና ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ፤ በአእምሮ ጤና መታወክ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በዓለም የአእምሮ ሕመም ስርጭት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ሰዎች ተጠቂ ሲሆኑ፤ በአህጉራችን በአፍሪካ ወደ 116 ቢሊየን ዜጎች ተጠቂ ናቸው፡፡
በፍርቱና ወልደአብ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ካሜሩን የመገናኛ ብዙሃን ስለ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ የጤንነት ሁኔታ ምንም ዘገባ እንዳይሰሩ አገደች
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የካሜሩ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ የጤንነት ሁኔታን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደረግ ክርክር እና ውይይት የተከለከለ መሆኑን የሀገሪቷ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፖል አታንጋ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ ማክሰኞ ጥቅምት ዕለት በጻፉት ደብዳቤ በፕሬዚዳንቱ ጤና ላይ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደረግ ክርክር እና ውይይት የተከለከለ መሆኑን በመግለጽ፤ ውይይት ሲያደርጉ የሚገኙ ሚድያዎችን በመከታተል ማቆያ ክፍል እንዲያስቀምጧቸው ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው የፕሬዝዳንቱ ሃሰተኛ የሞት ዜና የመገናኛ ብዙሃን መዘገቡን ተከትሎ ሲሆን፤ እነዚህ ሃሰተኛ ዘገባዎች ካሜሮናዊያንን በመረበሻቸው ነው ተብሏል፡፡
ደብዳቤው ለክልል አስተዳደር የተላከ ሲሆን፤ በአገሬው ፕሬዝዳንት ጤና ላይ የሚደረጉ ውይይቶች “የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ” መሆናቸውን በመግለጽ፤ ትዕዛዙን የሚጥስ ማንኛውም ሰው “ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚጠብቀውም ማስጠንቀቁን አልጀዚራ ዘግቧል።
የሀገሪቱ ጋዜጠኞች ይህ እገዳ የፕሬስ ነጻነትን የሚጋፋ ውሳኔ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ቢያ ለመጨረሻ ጊዜ የታዩት ከአንድ ወር በፊት በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ ጉባኤ ላይ ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኒውዮርክ የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሁም የፓሪስ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራት ጉባኤን ጨምሮ ሲጠበቅባቸው በነበሩት ስብሰባዎች ላይ አልተሳተፉም።
ከ40 ዓመታት በላይ በስልጣን የቆዩት የ91 ዓመቱ ፖል ቢያ፤ በአፍሪካ ውስጥ ከ 82ዓመቱ ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ ቀጥሎ በረጅም አገዛዝ ሁለተኛ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
አቤት ሆስፒታል የማስፋፍያ ፕሮጀክቱን ቦታ በፍርድ ቤት ክርክር አሸንፎ መረከቡን አስታወቀ
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌንየም ሕክምና ኮሌጅ ሥር የሚተዳደረው አቤት ሆስፓታል፤ ከሊዝ ነፃ ባገኘው 8926 ሜትር ካሬ ቦታ ላይ በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ ባለ አሥራ አምስት ወለል ሕንፃ ለማሠራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ፤ ቦታው ላይ የፍርድ ቤት ዕግድ ወጥቶበት ጉዳዩ በክርክር ላይ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡
ቦታው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት አዲሱ ገበያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፤ ለሌላ አግልግሎት ሲውል እንደነበር ተገልጿል፡፡
በፍርድ ቤቱ ክርክር ወቅት ተከራካሪው አካል ስምንት ሚሊዮን ብር እንዲያሲዚ ቢጠየቅም፤ ይህን ገንዘብ ለፍርድ ቤት ማስያዝ ባለመቻሉ ለሆስፓታሉ እንደተፈረደለት ተነግሯል።
እግዱን አውጥቶ የነበረው አካል ማረጋገጫ ካርታ የሌለው መሆኑ የፍርድ ቤቱን ክርክር እንዲያሸንፉ ዕድል እንደሰጠው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የግንባታ ክፍል ባለሙያው ገብረጊዮርጊስ ዘሩ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በዚም መሰረት ጳውሎስ ሆስፓቲል የማረጋገጫ ካርታ እንደተሰጠው ተገልጿል።
ተቋሙ አሁን ላይ የሕንፃው ግንባታ እንዲጀመር የጨረታ ሰነዱን አዘጋጅቶ ማስረከቡ የተነገረ ሲሆን፤ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥም የግንባታ ሥራውን ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙን አቶ ገብረጊዮርጊስ ለአሐዱ ገልጸዋል።
አቤት ሆስፒታል ሊያስገነባው ያሰበው አዲስ ሕንፃ ሲጠናቀቅ፤ ደረጃቸውን የጠበቁ 18 የቀዶ ሕክምናና 40 የማገገሚያ ክፍሎች፣ እንዲሁም ከ700 በላይ አልጋዎች የሚኖሩት ሲሆን፤ ለአስተዳደርና ለልዩ ልዩ ሥራዎች ማከናወኛ የሚውሉ በርካታ ክፍሎችን እንደሚይዝም ተገልጿል፡፡
በሚኪያስ ኃይሌ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
አካል ጉዳተኞችን አካታችን ለማድረግ የፖሊሲ ማዕቀፍ ማሻሻያ መደረግ አለበት ተባለ
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የአካል ጉዳተኞችን አካታችነትን ለማጎልበት፤ የፖሊሲ ማዕቀፍ ማሻሻል እና የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የሚመለከት አደረጃጀት (የመንግሥት መዋቅር) ማቋቋም እንደሚገባ የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ 23 ሚሊዮን የሚሆን አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ የገለጹት የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጄ፤ የግንዛቤ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ጉድለት፣ እንዲሁም የመረጃ ክፍተት ለአካል ጉዳኞችን ፈተና መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደ አብነትም የአካል ጉዳተኞች የህንጻ ተደራሽነት አዋጅ የጠቀሱ ሲሆን፤ አካል ጉዳተኞች ተደራሽ እና አካታች እንዲሆኑ በማድረግና በሁሉም መስኮች ላይ ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አካል ጉዳተኞች በተለያዩ ጉዳዮች ተካታች ለማድረግ ጥረት የሚደረጉ ጉዳተኞች መኖራቸውን እና ይህም እንደ መልካም መሻሻሎች ሊገለጹ ይችላሉ ሲሉም አክለዋል፡፡
እስከአሁን ኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞችን መብት ምላሽ የሚሰጥ ጥቅል አዋጅ እንደሌላት የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህን ለማድረግ ከወራቶች በፊት የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ወደ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መላኩን አንስተዋል።
አዋጁ ያሉትን ሕጎች ተከታትሎ የሚያስፈፅም፣ ካልተፈፀሙም ተጠያቂ የሚሆን ተቋም እንዲኖር ለማስቻልና የሕግ ክፍቶችም እንዲስተካከሉ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ የአዋጁን ተግባራዊነት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የአካል ጉዳተኞችን አካታችን ለማጎልበት የሕጎች ተፈጻሚነት ብቻ ሳይሆን ሕጎች እና የፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ ትኩረት ተሰቶ ሊሰራና ሊሻሻሉ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
በእሌሊ ግዛቸው
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የሶማሊያ፣ የኤርትራ እና የግብጽ መሪዎች ያደረጉትን ስብሰባ አስመልክቶ የጋራ መግለጫ አወጡ
ጥቅምት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋባዥነት፤ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ እና የግብፅ አረብ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ ትናንት መስከረም 30/2017 በአስመራ ከተማ ተገናኝተው የሦስትዮሽ ጉባኤ አካሂደዋል።
መሪዎቹ ስላደረጉት የሦስትዮሽ ጉባኤ አስመልክተው የጋራ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ በውይይታቸው በተለያዩ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም ቀጠናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ እና ትብብርን ለማጎልበት፤ መሰረታዊ መርሆችን እና የአለም ዓቀፍ ሕግ መሰረታዊ መርሆችን የማክበርን አስፈላጊነት አፅንዖት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የቀጣናውን ሀገራት ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበርና በውስጥ ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ የሚገቡትን ምክንያቶች መከላከል እንደሚያስፈልግ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።
መሪዎቹ ክልላዊ መረጋጋትን ለማስፈን እና ለሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የታለሙ የጋራ ጥረቶችን ለማስተባበር ቁርጠኛ መሆናቸውንም ባወጡት የጋራ መግለጫ ገልጸዋል።
የሦስቱ ሀገራት ትብብር እና ግንኙነት፤ የሶማሊያ መንግሥታዊ ተቋማትን ለማጠናከር እንዲሁም፤ የተለያዩ የውስጥ እና የውጭ ተግዳሮቶችን በመፍታት ረገድ ያላቸውን አቅም ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም የሦስትዮሽ ስምምነቱ ይገልጻል።
በተጨማሪም ጉባኤው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ በሱዳን እየተካሄደ ያለውን ቀውስ እና በአካባቢው መረጋጋት መፍጠር፣ በሶማሊያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልላዊ ለውጦች መፈጠርን አስመልክቶ እንዲሁም በቀይ ባህርና በባብ ኢል-ማንዳብ ባህር አዋሳኝ የባህር ዳርቻ ግዛቶች መካከል ያለውን ደህንነት ማስጠበቅ ዙሪያ መተባበር ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ስልታዊ የባህር መንገድ መገንባትን ማንሳታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሦስቱ ሀገራት መሪዎች የሶማሊያን መረጋጋት ለመደገፍ እና የሶማሊያን የፌደራል መንግሥት አቅም ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተስማምተውበታል፡፡
በተለይ ግብፅ ጦሯን በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር ጥረት እንድታደርግ ያቀረበችው ሀሳብ በሦስቱም በኩል ተቀባይነትን ያገኘ ሲሆን፤ መሪዎቹ የኤርትራ፣ የግብፅ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ያካተተ በሁሉም ዘርፎች ስትራቴጂካዊ ትብብርን የሚቆጣጠር የሦስትዮሽ ጥምር ኮሚቴ ለማቋቋም መስማማታቸውን በመግለጫው አስታውቀዋል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ኢትዮ ቴሌኮም በቀጣይ ሳምንት 10 በመቶ ድርሻውን ለሕዝብ መሸጥ እንደሚጀምር አስታወቀ
ጥቅምት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መንግሥታዊዉ የቴሌኮም አቅራቢያ ድርጅት ኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻዉን በቀጣይ ሳምንት ለሕዝብ መሸጥ እንደሚጀምር ተሰምቷል።
በኢትዮጵያ 130 ዓመታት ገደማ በመንግሥት በብቸኝነት ተይዞ የነበረዉን የቴሌኮም ዘርፍ፤ ከረቡዕ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለግል ባለሃብቱ በይፋ መሸጥ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange) አስር በመቶ ድርሻውን ለኢትዮጵያውያን እንደሚሸጥ በተደጋጋሚ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በጎፋ ዞን ለመሬት መንሸራተት አደጋ የተጋለጡ ከ600 በላይ ዜጎች ተለይተዋል ተባለ
ጥቅምት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ የመሬት መንሸራተት ስጋት አሁንም በመኖሩ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች መለየታቸውን የገዜ ጎፋ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም በቀበሌው የደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪ፤ በዞኑ የአደጋ መከላከል እና ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች የመለየት ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ የገዜ ጎፋ የመንግሥት የኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤቱ ኃላፊ የአለም መሪነህ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በዞኑ ከ800 በላይ ዜጎች ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ መሆናቸዉ እንደታወቀ የገለጹት ኃላፊው፤ ከእነዚህም መካከል ከ600 በላይ ዜጎች መለየታቸውን አስረድተዋል፡፡
አክለውም፤ ̎በአካባቢው በተደጋጋሚ በሚጥለው ዝናብ ምክንያት፤ ሙሉ በሙሉ ቤቶችን ለማደስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
ይህኝንም ተከትሎ ለመሬት መንሸራተት በይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ለ110 ሰዎች ቤት በመገንባት እንዲገቡ መደረጉን የገለጹ ሲሆን፤ በቀጣይ ከ300 በላይ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት በእቅድ መያዙንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡
አደጋውን ተከትሎ ዜጎችን በዘላቂነት የማቋቋምና በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ዜጎች የሥነ ልቦና ድጋፍ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ የአለም ጨምረው ተናግረዋል።
ሐምሌ 15/ 2016 ዓ.ም በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ በርካታ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ከ250 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል፡፡
አደጋውን ተከትሎ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በርካታ ሰብዓዊ ድጋፎች፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአደጋው ሕይታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን ለማሰብ ከሐምሌ 20 ቀን 2016 ጀምሮ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን መታወጁን አስታውቋል።
በእሌኒ ግዛቸው
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለማስቆም ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንደሚያስፈልጉ ተገለጸ
መስከረም 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ኮምሽነር ራኬብ መሰለ በዛሬው ዕለት ከአሐዱ መድረክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከአድማጭ ቤተሰቦች በርካታ ጥያቄዎች ተነስቶላቸዋል፡፡
"ኮምሽኑ በሚያወጣው ሪፖርት ለምን ለውጥ ማምጣት አልተቻለም?" እንዲሁም፤ "ፖለቲካዊ ችግሮችን መፍታት ካልተቻለ በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም አይቻልም" የሚሉ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
ተጠባባቂ ኮምሽነር ራኬብ መሰለ በምላሻቸው፤ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን መወሰን፣ ሕግን ማውጣት እንዲሁም ፖሊሲዎችን መቅረጽ እንደሚያስፍልግ ተናግረዋል፡፡
የተነሳላቸውን ጥያቄ መሰረት አድርገውም "በማህበረሰቡ ዘንድ ተስፋ መቁረጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው" ሲሉ አንስተው፤ ኮምሽኑ ሪፖርቱን አውጥቶ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ለፖሊስ እና እና ዐቃቤ ሕግ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
"የተቋሙ ሀላፊነት እርምጃ መወሰድ ሳይሆን ሪፖርቶችን ማውጣት ነው" ያሉት ተጠባባቂ ኮምሽነር ራኬብ፤ አህጉር ዓቀፍ እና አለም ዓቀፋዊ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲደረጉ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለማስቆም ተግባር ቀድም ሀላፊነት የመንግሥት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ሆነ ተቋም የተሰጠውን ሀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
"ኮምሽኑ የዜጎች እገታን ጨምሮ በብዙ ጉዳይዎች ላይ ሪፖርት እያወጣ በመሆኑ ያሉትን እድሎች መጠቀም ያስፍልጋል" ሲሉም አክለዋል፡፡
የቋሙ ዋና ሀላፊነት የሚፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ በማድረግ ማውጣት እንዲሁም፤ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሆነ ሁሉም ማሐበረሰብ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባም በአሐዱ መድረክ በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል፡፡
በፍቅርተ ቢተው
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ያሉትን ክፍቶች ለመለየት እንደሚያስችል ተገለጸ
መስከረም 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና በትናትናው ዕለት መመረጧ የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን ተጠባባቂ ኮምሽነር ራኬብ መሰለ በዛሬው ዕለት ከአሐዱ መድረክ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ያሉትን ክፍቶች ለመለየት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
"ከሰብዓዊ መብት አያያዝ እና ጥበቃ ጋር በተያያዘ ችግሮችን ከማየት ባለፈም ትምህርት የሚሰጥበት ነው" ብለዋል፡፡
"የምክር ቤት አባል መሆን፤ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታ የሚወሰንበት ነው" ያሉት ኮምሽነር ራኬብ፤ ሳውዲ ረቢያ ይሄን ዕድል አለማግኘቷንም አንስተዋል፡፡
"ይሄ ዕድል ያሉትን ችግሮች ለማስተካከል እና ለማሻሻል የሚረዳ ነው" ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት አንደኛ ፀሐፊ ከፍተኛ ዲፕሎማት ኩራባቸው ትርፌሳ ትናንት በኒውዮርክ በተካሄደው ምርጫ ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ከሚያስፈልጋት 97 ድምጽ 171 ድምጽ ማግኘቷን ገልጸዋል።
በምርጫው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ላይ የተመድ 193 አባል አገራት መሳተፋቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ለ3ኛ ጊዜ የተመረጠች ሲሆን፤ እ.አ.አ ከጥር 1/2025 አንስቶ እስከ 2027 ለሦስት ዓመት የምክር ቤት አባል ሆና እንደምታገለግል ተገልጿል።
ቦሊቪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ አይስላንድ፣ ሜክሲኮ፣ ኳታር፣ ሰሜን ሜቄዶኒያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ታይላንድ፣ ስፔን፣ ኮሎምቢያ፣ ቆጵሮስ እና ማርሻል አይላንድስ ሌሎች የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡ አገራት ናቸው።
በፍቅርተ ቢተው
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓመት ከ8 ነጥብ በላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስመዝግባለች መባሉ የተጋነነ ነው ተባለ
መስከረም 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የመንግሥትን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ባቀረቡበት ወቅት፤ በ2016 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ ጥቅል ሀገራዊ እድገት መመዝገቡን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አሐዱም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ይህን ያህል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ በሀገሪቱ ምቹ ኹኔታዎች አሉ ወይ? ሲል የምጣኔ ሐብት ባለሞያዎችን አነጋግሯል።
እንደ ሐገር ካልንበት ኹኔታ አንፃር ለዚህ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማደግ አዳጋች መሆኑንና በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ትልቅ ማነቆ መሆናቸው የተናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው አቶ እንዳይላሉ ሰለሞን ናቸው።
አቶ እንዳይላሉ፤ በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ ግጭቶች በመኖራቸው፣ የሥራ አጥ ቁጥር በመጨመሩ፣ የዋጋ ግሽበት በመናሩ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሠላም እጦት ምክንያት በበቂ ደረጃ ምርት ባለመስጠታቸው ምክንያት ይሄን እድገት ማስመዝገብ አይቻልም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አክለውም፤ "በሀገሪቱ ማምረት ከሚችሉ አካባቢዎች በጣም ጥቂቱ ናቸው የሚያመርቱት፡፡ ያሉትም ምርት በአግባቡ እየሰበሰቡ ነው የሚለው አጠያያቂ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "የተባለው እድገት ቢመዘገብም ያን ያህል አስደናቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን ብዙ ነገሮች እያሽቆለቆሉ ባለበት ሁኔታ የወጣው ሪፖርት በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል፡፡
ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላይኛው የምጣኔ ሐብት ባለሞያ፤ ከ 8 ነጥብ በላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንደ ሀገር ማስመዝገብ ካሉብን ችግሮች አንፃር አስቻይ አለመሆኑን ገልጸው፤ ዕድገቱ በገለልተኛ አካል አለመጣራቱን አንስተዋል፡፡
አክለውም "አጣሪውም ሪፖርት አቅራቢው መንግሥት ራሱ በመሆኑ ቁጥራዊ መረጃው የተጋነነ ያድርገዋል "ሲሉ ጠቁመዋል።
ባለሞያዎቹ ኢትዮጵያ የተባለውን ዕድገት የማስመዝገብ የአቅም ውስንነት እንደሌላት ታውቆ ኢኮኖሚ ላይ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በ2017 የበጀት ዓመት የ8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በወልደሀዋርያት ዘነበ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ:www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ከ3 በመቶ በላይ የሚሆነዉ የሕብረተሰብ ክፍል ለአይነስዉርነት ተጋላጭ መሆኑ ተገለጸ
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በአማካኝ እስከ 3 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆነዉ የሕብረተሰብ ክፍል ለአይነስዉርነት ተጋላጭ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ የተገለጸው የአይን ጤናን በሚመለከት በቀረበዉ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዉደ ጥናት ላይ ነዉ።
በአዉደ ጥናቱ በአማራ ክልል በተለይም በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን በተደረገ ጥናት ከ3 በመቶ በላይ የሚሆነዉ የሕብረተሰብ ክፍል ለአይነስዉርነት ተጋላጭ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም በኦሮሚያ ክልል ግላኮማ እና ትራኮማ በዋናነት ለአይነስዉርነት ከሚያጋልጡ የአይን በሽታዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለዚህም በዋናነት በዘርፉ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን፣ የግንዛቤ እጥረት እንዲሁም የአመራር እና የአስተዳደር ጉዳዮች እንደ ተግዳሮት ተጠቅሰዋል።
የአለም የጤና ድርጅት የዐይን ጤናን በሚመለከት ባወጣዉ መመሪያ እና ፖሊሲ መሰረት፤ በኢትዮጵያ የዐይን የጤናን በሚመለከት ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚተገበር አምስተኛውን ስትራቴጂክ ፕላን መጀመሩን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በፅዮን ይልማ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ለግሸን ማርያም ክብረ-በዓል ተጉዘው ወደ መጡበት መመለስ ያልቻሉ ከ2 ሺሕ በላይ ሰዎች አሁንም መፍትሔ አላገኘንም አሉ
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በየዓመቱ የሚከበረውን የግሸን ደብረ ከርቤ (ግሽን ማርያም) ክብረ-በአል በአካል ለመታደም ተጉዘው፤ መመለሻ መንገድ በማጣታቸው ምክንያት ወደመኖሪያ አካባቢያቸው መመለስ ያልቻሉት ዜጎች በደሴ ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ ተጠልለው በችግር ላይ መሆናቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል።
ለረሃብ እና ለበሽታ ተዳርገናል የሚሉት ተጓዦች በቁጥር ከ2 ሺሕ በላይ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ከወልዲያ፣ ከቆቦ፣ ከላስታ፣ ከዋግህምራ አካባቢዎች በዓሉን ለመታደም መምጣታቸውን ነግረውናል። ተጓዦቹ ወደ የመኖሪያቸው መመለስ ያልቻሉት ከደሴ ከተማ በኋላ ያለው መንገድ ለትራንስፖርት ክፍት ባለመሆኑ ምክንያት ነው። ብለዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከመስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በደሴ ከተማ በሚገኙ ቅ/ገብርኤልና መድኃኒዓለም ቤቴክርስቲያናት አካባቢ በመጠለያ ድንኳንና አዳራሽ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ሰምተናል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ እያዋጣ በሚሰጣቸው የዕለት ምግብ ቀናቸውን እየገፉ ቢሆንም እርዳታው በቂ ባለመሆኑ ለሕመምና ለርሃብ እየተዳረጉ እንደሚገኙበት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የደሴ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መፍትሄ እንዲሰጣቸው በአካል ቢጠይቁም መፍትሔ እንዳላገኙ የገለጹ ሲሆን፤ ̎ጥያቄያችንን በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር ለማስረዳት ብንሞክርም በተደጋጋሚ የምናገኘው ምላሽ አመራሮቹ ስብሰባ ላይ ናቸው የሚል ነው።̎ ብለዋል።
አሐዱ ለቅሬታው ምላሽ ለማግኘት የደሴ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ ነስረዲን ኃይሌን ለማነጋገር ባደረገው ጥረት፤ ከንቲባው ለጊዜው በአካባቢው እንደሌሉ እና መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በቀጣይ አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
በአለምነው ሹሙ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ቦይንግ በሥሩ ባሉ ተቋማት የሚሰሩ 17 ሺሕ ሠራተኞችን ሊያሰናብት ነው
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አሜሪካዊው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በሥሩ ባሉ ተቋማት የሚሰሩ 17 ሺሕ ሠራተኞችን በመቀነስ የድርጅቱን የሰው ኃይል በአንድ አስረኛ ሊቀንስ መሆኑን አስታወቀ።
ኬሊ ኦርትበርግ ለኩባንያው ሠራተኞች በላኩት የኢሜል መልዕክት ላይ፤ በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ ሥራዎች ሁሉ አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን ገልጸው፤ 17 ሺሕ ሠራተኞችን በመቀነስ የድርጅቱን የሰው ኃይል በአንድ አስረኛ ሊቀንስ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በድርጅቱ 33 ሺሕ ሠራተኞቹ በሥራ ማቆም አድማ የያዙት ቦይንግ የበላይ ኃላፊ ኬሊ ኦርትበርግ፤ “ቢዝነሳችን በአደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገኛል። እናም በጋራ የምንጋፈጠውን ተግዳሮት መግለጽ ከባድ ነው” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ኃላፊው አክለውም፤ ቦይንግ መሳርያዎች እና ወታደራዊ ቁሳቁሶች በሚያመርትበት ክንፍም ኪሳራ ሊገጥመው እንደሚችል በማሰብ፤ 777X የተሰኘውን አውሮፕላንን የሚያስረክብበትን ቀን አራዝሞታል ማለታቸውን ሮይተርሰ ዘግቧ።
እኤአ በ2018 እና በ2019 ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ የኢንዶኔዢያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ከተከሰከሱ በኋላ አውሮፕላኑ በመላው ዓለም ለ20 ወራት ከበረራ ታግዶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በቅርብ ጊዜም እንዲሁ የአላስካ አየር ማረፊያ ንብረት የሆነው 737 ማክስ አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ መስኮቱ መገንጠሉን ተከትሎ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
አምስት ኑክሌር የታጠቁ ሀገራት በኒውዮርክ ስብሰባ ሊያደርጉ ነው
ጥቅምት 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አምስት ኑክሌር የታጠቁ ሀገራት ቡድን በሚቀጥሉት ኹለት ሳምንታት ውስጥ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ስብሰባ ሊያደርጉ መሆኑን የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ርያብኮቭ ገልጸዋል።
በዚህ ስብሰባ ኑክሌር የታጠቁት እና የተመድ የጸጥታው ምክርቤት ቋሚ አባል የሆኑት ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና እና እንግሊዝ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
ርያብኮቭ ስብሰባው የሚካሄድበትን ቀን በትክክል አልጠቀሱም የተባለ ሲሆን፤ ሀገራቱ በምን ኃላፊዎች ደረጃ እንደሚሳተፉም ግልጽ አለማድረጋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ በሩሲያ እና በምዕራባዊያን መካከል ያለው ውጥረት እያየለ በመምጣቱ ስብሰባው አስፈላጊ ነውም ተብሏል።
ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ የኑክሌር የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ፖሊሲዋን መቀየሯን መናገራቸው ይታወሳል።
ሞስኮ በአዲሱ የኑክሌር አጠቃቃም ፖሊሲዋ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም የምትችልባቸውን ሁኔታዎች በዝርዝር አስቀምጣለች።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
መንግሥት በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የቡናው ዘርፍ ላይ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን ቡና ላኪዎች ማሕበር ተናገረ
ጥቅምት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በመላክ ዶላር ከምታገኝባቸው የወጪ ምርቶች መካከል የቡናው ዘርፍ ቀዳሚው ቢሆንም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በውል እንዳልተመለከተው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማሕበር አስታውቋል።
ቡናን ከገበሬ ተረክበው ወደ አውሮፓ፣ እስያና አረብ አገራት በመላክ የተሰማሩት ቡና ላኪዎች የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው በሥራችን ላይ ተፅዕኖ አሳድሮብናል ብለዋል።
ማሕበሩ እንደገለጸው፤ በውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ወደ ውጭ የሚልኩ ቡና ላኪዎች ብሔራዊ ባንክ አስገዳጅ መመሪያ እንዲሻሻል በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ የቡና ምርቷ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ከሆኑ የግብርና ምርቶች አንዱ መሆኑን የሚታወቅ ቢሆንም፤ ብሔራዊ ባንክ በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ያወጣውን መመርያ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማሕበር ስራ አስፈፃሚ ግዛት ወርቁ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ ለአገር ውስጥ የሚውሉ የቡና ምርቶች አቅርቦት እጥረት እንዲፈጠርና የቡና ገበያው ላይ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ቡና ላኪዎች ምርት ለማግኘት እየተቸገሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጥ ሲሉ የቡና ላኪዎች ማሕበር ሥራ አስፈፃሚ ግዛት ወርቁ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ባለፈው በጀት ዓመት 1.43 ቢልየን ዶላር ከቡና የተገኘው የውጭ ምንዛሪ፤ በታሪክ ቀዳሚው ሆኗል ማለቱን ከተቋሙ ባገኘነው መረጃ ተመልክተናል።
ወደ ውጭ መዳረሻ አገራት ገበያ የቀረበውን ቡና ምንም እንኳን የበለጠ አሐዝ እንዳለው ቢገለጽም፤ በዘርፉ መፍትሔ ሚመሹ ጉዳዮች መኖራቸውን ከማሕበሩ ሰምተናል።
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ጤና ሚኒስቴር የታዳሽ ሀይልን በጤናው ዘርፍ መጠቀም የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ
ጥቅምት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ባለባቸዉ አካባቢዎች በጤናው ዘርፍ ታዳሽ ሀይልን መጠቀም መጠቀም የሚያስችል ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት በጤና ሚኒስቴር ይፋ ተደርጓል።
ጤና ሚኒስቴር ከአለም ጤና ድርጅት እና ከተባበሩት መንግሥታት የህጻናት አድን ድርጅት ጋር በመተባበር ኤለክትሪክ ሃይል እጥረት ባለባቸው በተመረጡ የመንግሥት ጤና ተቋማት ታዳሽ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሻሻል ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህንን ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የማስጀመር መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡
በፕሮጀክቱ ለ300 ጤና ተቋማት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ፤ ከ6.7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎም እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ በኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ፓኪስታን የሚተገበር ሲሆን፤ ለዚህ ማስፈፀሚያም 35 ሚሊየን ዶላር መመደቡም ተነግሯል፡፡
በማስጀመሪያ ፕሮግራሙም የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጨምሮ፤ ሚኒስቴር ዴኤታዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የሆስፒታሎች የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ድርጅቶች ተገኝተዉበታል፡፡
በፅዮን ይልማ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የፖስፖርት የግዜ ቆይታ ከአምስት ዓመት ወደ አስር ዓመት ከፍ ማለቱ ተገለጸ
ጥቅምት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢሚግሬሽን ዜግነትና አገልግሎት የፖስፖርት የግዜ ቆይታ ከአምስት ዓመት ወደ አስር ዓመት ከፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ፖስፖርት ለማደስ አምስት ዓመት ይጠበቅ እንደበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ከአንድ ወር በኃላ ወደ ሥራ በሚገባዉ አሰራር መሰረት ግን ከ25 ዓመት በላይ ለሆናቸው ዜጎች በየ10 ዓመቱ እንደሚታደስ አገልግሎቱ ገልጿል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ ካደረጉ ቀዳሚዎቹ የሆነዉ የኢሚግሬሽን ዜግነትና አገልግሎት በፖስፖርት ላይ ጭማሪ ማድረጉ አይዘነጋም።
ተቋሙም ማሻሻያዉን ካደረገ በኃላ በሩብ ዓመት አፈፃፀሙን በተመለከተ በዛሬዉ ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
በመግጫዉም ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊ ዳዊት በሦስት ወራት ዉስጥ ለ22 ሺሕ ዜጎች አስቸኳይ ፖስፖርት መስጠቱን ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ ከፖስፖርት ጭማሪ ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸዉ ጥያቄ፤ "ዋጋ ጭማሪዉ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር በጣም ትንሹ ክፍያ ነዉ̎ ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 4 መቶ 78 ሺሕ የሚሆኑ ፖስፖርቶች ከዉጭ ማስገባቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ለ357 ሺሕ ደንበኞች የማስተላለፍ ሥራ ተሰርቷል ተብሏል።
ከነሐሴ ወር ጀምሮ ለ22 ሺሕ ዜጎችም አስቸኳይ ፖስፖርት መስጠቱን የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታዉቋል።
በተጨማሪም የአቅም ዉስንነትን ከመቅረፍ አኳያ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል ተብሏል።
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በመዲናዋ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ አምራቾች በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ረገድ ችግር እየፈጠሩ ነው ተባለ
መስከረም 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ አምራቾች በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ረገድ ችግር እየተስተዋለባቸው እንደሚገኝ የከተማ መስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።
ባለስልጣኑ እንደገለጸው፣ በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ረገድ ችግር የተስተዋለባቸወ በመዲናዋ ፋብሪካ ተክለው በአምራችነት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ሲሆኑ፤ የሚያመነጩት በካይ ጋዝ በፈሳሽ መልኩ የወንዝ ዳርቻዎችን እየበከለ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ባለስልጣኑ ወቀሳ የሰነዘረባቸውን የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ፋብሪካዎች በሥም ባይጠቅስም፤ ̎የፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻን ጨምሮ የኬሚካል አወጋገድ የሚጠቀሙበት መንገድ ከአቅም በታች ነው̎ ብሏል።
አምራቾቹ የፈሳሽ ኬሚካል አወጋገድ ስርዓታቸውን እንዲያሻሽሉ በተደጋጋሚ ምክረ ሐሳብ ሲሰጣቸው የቆየ ቢሆንም፤ ማሻሻል ባለመቻላቸው እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ባለስልጣኑ ለአሐዱ ገልጿል።
ይህን ለአሐዱ የነገሩት በአዲስአበባ ከተማ መስተዳድር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ኃላፊ ስናይት ተስፋዬ ናቸው።
ባለስልጣኑ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ዙርያ ጥናት አስጠንቶ ተግባራዊ አድርጎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም ጥናት በአዲሱ በጀት ዓመት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በተለይም የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ያሉ እክሎች በማህበረሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያሳድሩ መሆኑን ኃላፊዋ ነግረውናል።
በመዲናዋ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያመነጩት ኬሚካል ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ ችግሩን መፍታት እንዳልተቻለም ጨምረው ገልጸዋል።
ይሁንና ከችግሩ ስፋት አንፃር በተፈለገው ልክ መፍታት እንዲቻል፤ ፋብሪካዎቹ የሚቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ እየተጠየቀ እንደሚገኝም ከኃላፊዋ መረዳት ችለናል።
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ፕሬዝዳንቶች የተሰጣቸው ፓለቲካዊ ሚና የዲሞክራሲ ምሕዳሩ መጥበብ ማሳያ መሆኑን ተገለጸ
መስከረም 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲዊ ሕገ-መንግሥት ለፕሬዝዳንቶች በሰጠው ሚና በፓለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ መገደቡ፤ ለዲሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች መቀጨጭ አይነተኛ ማሳያ እንደሆነ ለአሐዱ ሐሳባቸውን የሰጡ የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የሕግ ባለሙያዎቹ "ሁሉም የፓለቲካ ውሳኔዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ላይ ብቻ በመሰጠታቸው የሐሳብ ገበያው ምሕዳር እንዲጠብ ለማድረጉ በቅርቡ የተሰናበቱት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ማሳያ ናቸው፡፡" ብለዋል፡፡
በንፅፅር ከሌሎች ፌዴራል ስርዓት አራማጅ ሀገራት አንፃር በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የፕሬዝዳንትነት ሹመት የሚሰጠው ጥቅም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ-ሥላሴ የስልጣን ዘመንም የተለየ ነገር እንደማይጠብቁ ለአሐዱ የተናገሩት የሕግ ባለሙያው ታምራት ኪዳነማርያም ናቸው።
የሕግ ባለሞያው ታምራት፤ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሕገመንግሥቱ የተገደበውን የመጫወቻ ሜዳ፤ በመጠኑም ቢሆን ለማስፋት ጥረት አድርገዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ቀደም ያሉ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንቶች በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተተወው የተለጠጠ ስልጣን አሉታዊ ጫና ሲያጠላበት እንደነበር አስታውሰው፤ ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰላም እንዲወርድ የነበራቸው ጥልቅ ፍላጎት የሚደነቅ መሆኑንም ለአሐዱ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ ተሿሚዎች በፓለቲካው የነበራቸው ተሳትፎ አነስተኛ ሆኖ በመቆየቱ ሳቢያ፤ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩንም አቶ ታምራት ገልጸዋል።
የፕሬዝዳንት ስልጣን ዲፕሎማሲ ተኮር መሆኑ በሕገ-መንግሥቱ ላይ መሻሻል ከሚገባቸው አንቀጾች መካከል አንዱ መሆን እንደሚገባው ያሳሰቡት ደግሞ፤ ሌላኛው የሕግ ባለሙያ አቶ አበባው አበበ ናቸው።
የሕግ ባለመያው አበባው በበኩላቸው ተሿሚው ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ በአገረ መንግሥት ግንባታና ኢትዮጵያ አልፎ አልፎ እየገጠማት ያለውን የዲፕሎማሲ እክል አስፈላጊውን መፍትሔ እንዲመጣ በትኩረት ይሰራሉ ብለው እንደሚያምኑ ነግረውናል።
የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ረቆ ሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ ባሉ ጊዜያቶች ውስጥ፤ አዲሱ ተሿሚ ታዬ አፅቀ-ሥላሴን ጨምሮ ስድስት ፕሬዝዳንቶች መሾማቸውን ይታወቃል።
ሆኖም በኢትዮጵያ የፓለቲካ ስርዓት ያመጡት አንዳች ለውጥ እንደሌለ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። ለዚህም የበርካታ ትችቶች ምንጭ ሲሆን መቆየቱን ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያዎች አመላክተዋል።
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በአርባምንጭ ከተማ አንድ ሊተር ቤንዚን ከ250 ብር በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ተገለጸ
መስከረም 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ የሚገኙ ማደያዎች ለሦስት ሳምንት ከዋናው የጁቡቲ ማሰራጫ ነዳጅ ስላልቀረበላቸው፤ ቤንዚን በሊተር ከ250 እስከ 300 ብር እየተሸጡ እንደሚገኝ በከተማዋ የሚገኙ አሽከርካሪዎች ለአሐዱ ተናግረዋል።
ቅሬታቸውን ለአሐዱ የገለጹት አሽከርካሪዎቹ፤ በሁሉም ማደያዎች በሚባል ደረጃ ቤንዚን እንደማይገኝ ገልጸው፤ ሥራቸውን ለማከናወን ሲሉ በሕገወጥ መንገድ ከሚነግዱ ነጋዴዎች ላይ ለመግዛት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ለከፋ ችግር፤ አለፍ ሲልም ሥራ ለማቆም በገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡
በከተማዋ ቤንዚን በቤርሜል፣ በጀሪካን እንዲሁም በፕላስቲክ ጠርሙሶች እየተሸጠ እንደሚገኝ የገለጹት አሽከርካሪዎቹ፤ ̎̎̎̎እርሱም ከወጣለት ተመን በላይ በሊትር ከ250 እስከ 300 ብር እየተሸጠ ይገኛል̎ ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አሐዱም የቅሬታ አቅራቢዎቹን ቅሬታ በመያዝ የከተማው ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤትን አነጋግሯል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ተመስገን ሰይድ በምላሻቸው፤ በከተማው ለሚገኙ ማደያዎች ከዋና ማከፋፈያ ፕሮግራም ስላልወጣላቸው የቤንዚን እጥረት እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ከዚህን ቀደም የገቡ ነዳጆችን ማደያዎች በመደበቅ፤ እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ በሽያጭ ለተሰማሩ ነጋዴዎች በማቅረብ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም በከተማዋ ቤንዚን በተባለውና ከዚያ በላይ በሆነ ዋጋ እየተሸጠ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
አሐዱ አያይዞም ችግሩን መኖሩ ከታወቀ የቁጥጥር ሥራዎች ለምን አልተሰሩም? በቁጥጥር ሂደት ወቅት የተወሰዱ እርምጃዎችና መፍትሔ ሀሳቦችስ አሉ ወይ?̎ ሲል የጠየቀ ሲሆን፤ ኃላፊው ችግሩን ለመቅረፍ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ በዚህም የቁጥጥር ሥራ በሁለት ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
በአክለውም፤ በቅርብ ቀናት ውስጥ በከተማዋ የሚስተዋለው ሕገ ወጥ የነዳጅ ንግድ እንቅስቃሴ እንደሚፈታ አመላክተዋል።
በከተማው በተለያዩ ጊዜያት መሰል ጉዳዮች የሚነሱ ናቸው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስከረም 28/2017 ጀምሮ በሥራ ላይ የሚውል የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጥማሬ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በጭማሬውም መሰረት በሁሉም ማደያዎች፤ ቤንዚን በ91.14 ብር፣ ነጭ ናፍጣ በ90.28 ብር፣ ኬሮሲን በ90.28፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በ100.20፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በ97.67 እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ በ77.76 ብር በሊትር እንዲሸጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
በወልደሀዋርያት ዘነበ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
"የጸጥታ ኃይሉን ጭምር የከፈለ ልዩነት ነው የተከሰተው" በትግራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች
መስከረም 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቶ ከፓርቲዎች ወደጸጥታ ኃይሎች ጭምር በመከፋፈል የዶክተር ደብረፅዮን እና የአቶ ጌታቸው ረዳ የሚል ታማኝ ኃይል አዘጋጅተዋል ሲሉ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
ከአሐዱ ጋር ቆይታ የነበራቸው የአረና ትግራይ ፓርቲ ዋና ሊቀመንበር አቶ አምዶም ገብረስላሴ፤ "የሁለቱም አካሄድ የስልጣን የሚመስሉ አካሄዶች አሉት" ብለዋል፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ "ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች በአንድ ዕዝ የመመራት ችግር አለባቸው" ያሉ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ የፖለቲካውን ውድቀት የሚያሳይ ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም በክልሉ መካረር ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች እንዲሳተፉ የሚያደርግ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸው፤ "ከፍተኛ እና መካካለኛ አመራሮች ወደ አንዱ አካል የመወገን ሁኔታ ይታይባቸዋል" ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሠራዊቱ አባላት ጦርነት ዉስጥ የቆዩ በመሆኑ ምንም ዓይነት ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የላቸውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"ለመሆኑ ይህ የመከፋፈል ሁኔታ ዳግም በክልሉ ግጭትን አያስነሳም ወይ?" ሲል አሐዱ ላነሳላቸው ጥያቄ፤ ይህ ሁኔታ ወደ ጦርነት እንደማይገባ ዕምነት እንዳላቸው ገልጸው፤ እንደ ምክንያትም "ፖለቲከኞቹ ወደ ለየለት ሁኔታ ውስጥ ገብተው ስልጣናቸውን የማጣት ፍላጎት የላቸውም" ብለዋል፡፡
የባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ በርሄ በበኩላቸዉ፤ "ሁለቱ ቡድኖች እያደረጉት ያለው ሁኔታ ከስልጣን አልፎ ወደ አካባቢያዊ ሁኔታ ውስጥ እየቀየሩት ይገኛሉ" ብለዋል፡፡
በዚህም "ልዩነቱ ሰፍቶ ወደ ሕዝብ ለማጋባት እየተሰራ ያለው ሁኔታ ተገቢነት የሌለው ነው" ሲሉም አሳስበዋል፡፡
"የጸጥታ ሃይሉ የጊዚያዊ አስተዳደር ሥር የተቋቋመ አንድ ካቢኔ ነው እንጂ የፓርቲ አይደለም" ያሉት አቶ ዮሴፍ፤ "ገለልተኝነት ለማሳየት የሚደረገው ጥረት ተገቢ አይደለም" ብለዋል፡፡
አክለውም፤ "ጸጥታ አስተዳደሩ የጊዚያዊ አስተዳደር የሚመጣን ሥራ የመስራት ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ፤ ይህንን ሊያርም ይገባል" ሲሉ አቶ ዮሴፍ ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው ሰኞ መስከረም 27/2017 በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓት ባወጣው መግለጫ፤ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚገኙባቸው 13 የጊዚያዊ አስተዳደሩ የሥራ ሃላፊዎች በማንሳት በሌሎች 14 የድርጅቱ አባላት እንዲተኩ መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የህወሓቱ ቡድን በግልፅ "መፈንቅለ ስልጣን እንዲደረግብኝ አውጇል" ያለ ሲሆን፤ "የጥፋት ኃይል" ባለው ቡድን ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር አስታውቋል።
የትግራይ ጸጥታ ኃይል በበኩሉ በህወሓት አመራሮች መከፋፈል ምክንያት ከሁለቱም አካላት የሚወጡ መግለጫዎች በሕዝቡ ውስጥ የመረበሽ ስሜት መፍጠራቸውን ገልጾ፤ "መግለጫዎቹ ምክንያት የሚፈጠር ማንኛውንም አይነት ስርዓት አልበኝነት ተቀባይነት የለውም" ማለቱ ይታወሳል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በመዲናዋ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ4 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 7 ሰዎች ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው
መስከረም 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከጎሮ ወደ ኮዬ ፈቼ በሚወስደው መንገድ ላይ አርሴማ በተባለ አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ፤ የ4 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 7 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፤ ኮድ 3 ታርጋ 69867 ቱርቦ ገለባጭ መኪና በአይሱዙና በከተማ አውቶቢስ ላይ ባስከተለው የመኪና አደጋ የሰዎች ሕይወት ማለፉንና በአካል ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በአደጋውም የአውቶቢስ ትኬት ለመቁረጥ የቆሙ 3 ሴቶችን እና በአካባቢው ላይ በጉሊት ንግድ የምትተዳደር ነጋዴ ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ ሹፌሩን ጨምሮ ሌሎች በአካባቢው የነበሩ 7 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡
ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 7 ሰዎችም በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ጨምረው ለአሐዱ አስታውቀዋል፡፡
በዳግም ተገኝ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ:www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ