ጦርነት እንዲቆም እና ሰላም እንዲሰፍን ከመንግሥት በላይ እየተጨነቅን ያለነው እኛ ነን ሲሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለጹ
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በዋነኛነት ሀላፊነቱን የሚወስዱት መንግሥትና ጠበንጃ አንስተው የሚዋጉ ሀይሎች ቢሆንም፤ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሰላም የተለያዩ ጥሪዎችን በማቅረባችን በመንግሥት እንደ ጠላት እየተቆጠርን ነው ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ገልጸዋል።
"ጦርነት እንዲቆም ሰላም እንዲሰፍን ከመንግሥት በላይ እየተጨነቅን ያለነው እኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነን" የሚሉት የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ አብርሃም ሀይማኖት፤ "መንግሥት የሆነው አካል 'ማንም ሺሕ ዓመት ቢዋጋ አያሸንፈንም' ከማለት ውጪ በተግባር የተደገፈ ቁርጠኛ የሆነ የሰላም ጥሪን አለማድረጉን በፖለቲካል ግምገማችን ግምግማናን" ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ኮሚቴ ቢቋቋምም ያለው ነባራዊ እውነታ ግን የሚፈለገውን ሰላም እንዳላመጣ የጠቆሙም ሲሆን፤ "መንግሥት ሁሉንም ችግር በጦርነትና በጉልበት ለመፍታት የሚጓዝ ሁኗል" ሲሉም ተናግረዋል።
"ለፖለቲካ ችግሮቻችን ፖለቲካዊ መፍትሄ እንጂ፤ የሀይል አማራጭ መሆን የለበትም" የሚሉት የእናት ፓርቲ ፕሬዝደንትና የትብብር ፓርቲዎች የወቅቱ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው ናቸው፡፡
ዶ/ር ሰይፈስላሴ አክለውም፤ "ከመንግሥት ጋር ያለው ችግር ሁሉንም ነገር በሀይል እደፈጥጠዋለሁ፣ እመልሰዋለሁ የሚል እሳቤ ነው፣ ይህ ደግሞ ከቀደመው ታሪካችን መማር አለመቻላችንን የሚያሳይ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
"ሰላም እንዲሰፍን ከመንግሥትና ታጣቂ ሀይሎች በበለጠ ሁኔታ ልንሰራ የምንችለው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እኛ ጠበንጃ የለንም፣ በሰላማዊ መልኩ የምንታገል የፓለቲካ ፓርቲ ነን" የሚሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በሀገሪቱ ሰላማዊ እንዲመጣ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝና ወደፊትም ሀገር ሰላም እስክታገኝ ድረስ እንደሚቀጥሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
"የአይበገሬነት ስሜት መንግሥት ውስጥ አለ፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር ለማንም አይጠቅምም፣ ቅንነቱና ፍላጎቱ ካለ አሁንም አልረፈደም" ያሉም ሲሆን፤ "የፖለቲካ ችግሮችን ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ መንግሥት የራሱን ግንባር ቀደም ሚና መጫወት አለበት" ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን ቀንን ከማክበር ባለፈ በጤናው ዘርፍ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን መሙላት ያስፈልጋል ተባለ
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ነገ ታሕሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም "የመንግሥት ኃላፊነት ለጤና" በሚል መሪ ቃል "ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ቀን" ይከበራል።
በኢትዮጵያም ቀኑ ከሕዳር 30 እስከ ታሕሳስ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ፤ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
አሐዱም "የጤና ሽፋን ቀንን ከማክበር እና ቀኖችን ስያሜ ከመስጠት ባለፈ ምን መሰራት አለበት? በዘርፉስ ምን ምን ችግሮች አሉ?" ሲል፤ የኢትዮጵያ የሕክምና ማህበርን እና የጤና አጠባበቅ ማህበርን ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕክምና ማህበር ፕሬዝደንት ዶክተር ተግባር ይግዛው በሰጡት ምላሽ፤ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሲባል፤ ማንኛውም ሰው አቅሙን ያገናዘበ የጤና አገልግሎት ማግኘት ማለት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ "ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው አማካይ የጤና አገልግሎት መለኪያ 65 ጋር ሲስተያይ፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ደረጃ 35 ነው" ብለዋል፡፡
"በአፍሪካ ያለውም ሲታይ 44 ነው" የሚሉት ዶክተር ተግባር፤ "በኢትዮጵያ ግን ሁሉን አቀፍ የሆነ የዜጎች የጤና መድህን ሽፋን አለመኖር፤ አንድ ሰው ታሞ ለመታከም ቢሄድ ከአቅሙ በላይ ገንዘብ እንዲጠየቅ የሚያደርግ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም ቀኑን አስቦ ከመዋል ባለፈ፤ ብቃት ያላቸውን የጤና ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ማመቻቸት፣ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ መድሃኒቶችን በየጤና ተቋማቱ ማቅረብ እንዲሁም በቂ ፋይናንስ መመደብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማህበር በበኩሉ፤ "ስለ ጤና አጠባበቅ እና በጤና ተቋማት ላይ ያሉ ጉዳዮችን የሚመለከቱ የተፃፉ አሰራሮችን ወደ መሬት ማውረድና እናቶች እና ሕጻናትን ከሞት መታደግ እንዲሁም የመድሃኒት አቅርቦት ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል" ብሏል፡፡
"መከላከልን መርህ ያደረገ ፖሊሲን እንከተላለን ይባል እንጂ አተገባበሩ ላይ ክፍተት አለ። ስለዚህ የበጀት ምደባ፣ የሰው ሀይል ትኩረት እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ መሰራት አለበት" የማህበሩ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር አርጋው አምበሉ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
አሐዱም "ችግሮችን ፈቶ መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ በሚሰራው ሥራ ችግር የሆኑ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?" የሚለውን የጤና ሚኒስቴርን ለመጠየቅ ቢሞክርም፤ ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ አልተሳካም፡፡
በእመቤት ሲሳይ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
"በአዲስ አበባ ለቀናት የነበረው ተኩስ የሕዝብን ሥነ ልቦና ለመስለብና ለማስፈራራት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው" የትብብር ፓርቲዎች
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመንግሥት እና በኦነግ ሸኔ ከፍተኛ አመራር በሆኑት ጃል ሸኚ መካከል ተፈረመ የተባለውን ስምምነትን ተከትሎ፤ ወደ ተሃድሶ ማዕከላት በማቅናት ላይ የነበሩ የቡድኑ አባላት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ለሦስት ቀናት ባደረጉት ተኩስ የአንዲት ሴት ሕይወት ማለፉ ይታወቃል።
ፖሊስ ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫም፤ ታጣቂዎቹ አዲስ አበባ ከተማን አቋርጠው ወደ ስልጠና ማዕከላት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እየጨፈሩና የደስታ ስሜት እያሰሙ ሲንቀሳቀሱ የተኩስ ድምጽ በማሰማታቸው በከተማው ነዋሪ ሕዝብ ላይ ድንጋጤና መረበሽ ሊፈጠር መቻሉን ገልጾ ነበር።
በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከፍተኛ ጥንቃቄና የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም አስታውቋል።
በዚህም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እንዲሁም እናትፓርቲ በዛሬው ዕለት ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለበዓላት እንኳን ርችት እንኳን እንዳይተኮስ በከለከለበት ሁኔታ ሙሉ ትጥቅ ተይዞ መግባት መቻሉ ጥያቄ ፈጥሮብናል" ብለዋል።
የትብብር ፓርቲዎቹ አክለውም "ስምምነቱ ጥርጣሬ አጭሮብናል" ያሉ ሲሆን፤ ከስምምነቱ ግልጸኝነት ማጣት በተጨማሪም "ስምምነቱ መሣሪያ ማውረድን አይጨምርም" በማለት ጠይቀዋል።
"የአንድም ሰው የሰላምን መንገድ መምረጥ ያስደስተናል" ያሉት ፓርቲዎቹ፤ "ነገሮችህን አደባብሶ ማለፉ ግን አሳሳቢ ነው" ሲሉ ተችተዋል።
ለአብነትም ኤርትራ በረሃ ከኦነግ ጋር በክልል አመራሮች ደረጃ ግልጽነት የጎደለው ስምምነት ከተደረገ በኋላ የሰላም ተፈራራሚው ኃይል "ቃል የተገባልኝ አልተፈጸመም" በሚል ሰበብ ተመልሶ ጫካ መግባቱን ሕዝቡም ሰላም ማጣቱን አስታውሰዋል።
ስለሆነም መንግሥት የስምምነቱን ሂደትና ዝርዝር ነጥቦች "የመከራው ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ" ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ሲሉ አሳስበዋል።
"በየተኩስ እሩምታ ሰበብ መገናኛ አካባቢ ለተገደሉት እናት መንግሥት ኃላፊነት እንዲወስድና ቢያንስ ቤተሰባቸውን ይፋዊ ይቅርታ በመጠየቅ ተገቢውን ካሳ ሊከፈል ይገባል" ብለዋል።
አክለውም ለቀናት የዘለቀው ተኩስ፣ በሰላም ስምምነት የመጣ ሳይሆን፤ ሆን ተብሎ የሕዝብን ሥነ ልቡና ለመስለብና ለማስፈራራት የተደረገ መሆኑን "ሕዝባችን እንዲያውቀው እንሻለን" ሲሉ አጽኖዖት ሰጥተዋል።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ሚኒስቴሩ ከ5 ዓመታት በፊት በአማራ ክልል ፎገራ ወረዳ እየተገነባ የነበረውን የመስኖ ፕሮጀክት አፈፃፀም ዙርያ ቅሬታ ተነሳበት
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከአምስት ዓመታት በፊት በአማራ ክልል ፎገራ ወረዳ እየተገነባ የነበረውን የመስኖ ፕሮጀክት አፈፃፀም ዙርያ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅሬታ ተነስቶበታል።
ፕሮጀክቱ ምግብን በራስ የመቻል ህልም ተወጥኖለት የነበረ ቢሆንም፤ ምክንያቱ ባልታወቀና ግልፅ ባልሆነ መንገድ መጓተቱ ጥያቄ አስነስቷል።
ይህ የተገለጸው የሕዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት በትናንትናው ዕለት ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው።
"በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ይገነባል ተብሎ የታሰበው ይኸው የመስኖ ፕሮጀክት የተጓተተበትን ምክንያት ለማጣራት ብንሞክርም በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ መስተናገድ አልቻልንም" ሲሉ የሕዝብ እንደራሴዎቹ በምክር ቤቱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች የተጓተቱ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የቆላና መስኖ ሚኒስትር ምላሽና ማብራርያ እንዲሰጥበትም ሚኒስትሩን አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ጠይቀዋል።
ፕሮጀክቶች በአብዛኛው ለውጭ ኩባንያዎች ተሰጥተው የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ላይ ለአገር ውስጥ ተቋራጮች እንዲሰጡ መደረጉን የምክር ቤት አባላቱ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በቀጣይ ስኬታማ ሥራ መስራት የሚያስችለውን አዲስ ተቋማዊ አደረጃጀት የዘርፉ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች በአግባቡ እንዲተገብርም አባላቱ ማሳሰብያ ሰጥተዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ለፕሮጀክቶች አፈጻጸም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራምና ሐላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከእንደራሴዎቹ ተጠይቋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በምላሻቸውም ከአምስት ዓመታት ወዲህ ባሉ ጊዜያት ውስጥ ከ112 በላይ መስኖ ነክ ፕሮጀክቶች መምከናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ የተጀመሩትን የመስኖ ፕሮጀክቶች በተገባው ውል መሰረት ለማጠናቀቅ እስከ 40 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በመግለጽም፤ ለሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ግን የተያዘው በጀት 8 ቢሊዮን ብቻ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በዚህም የበጀት እጥረት ምክንያት ለጊዜው አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መያዝ እንደማይቻልና ቀደም ሲል ከታቀዱት ውስጥ ደግሞ 8 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለጊዜው የጨረታ ሂደታቸውን ለማቋረጥ እንደተገደዱ ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያከናወነ ሲሆን፤ የደረቅ ቆሻሻ አጠቃቀምና አወጋገድ የተመለከተው ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቶ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በአማኑኤል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በአማራ ክልል ከ30 በላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የፀጥታ አባላት በታጣቂ ሃይሎች መገደላቸው ተነገረ
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ባለፈው ሳምንት ከ30 በላይ የአካባቢው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የፀጥታ አባላት በክልሉ በሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የአካባቢው አስተዳደር ተናገሩ።
በዞኑ ደጋ ዳሞት ወረዳ "ፈረስ ቤት" ከተማ ሕዳር 26/2017 ዓ.ም. ለሁለት ወራት ለመንግሥት ኃይሎች "መረጃ እና ድጋፍ ሰጪ" በሚል ተጠርጥረው በታጣቂዎቹ ተይዘው የነበሩ በርካታ የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት "መረሸናቸውን" ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አለማየሁ 20 ከሚሆኑ የወረዳው ካቢኔዎቻቸው ጋር የግድያው ሰለባ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።
መስከረም መጨረሻ በአካባቢው "ከባድ ውጊያ" መደረጉን ተከትሎ፤ መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ወረዳው በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር መግባቱን እና የመንግሥት ኃይሎች ወረዳውን ለቀው መውጣታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ "[መከላከያ] የሚሊሻ፣ የፖሊስ አባላትን እንዲሁም ካቢኔዎችን በሙሉ መስመር ላይ ነው ጥሏቸው የሄደው" ሲሉ አንድ ነዋሪ፤ 'ባልተለመደ ሁኔታ' የወረዳው አስተዳደር ከተማዋ ውስጥ መቅረቱን ገልጸዋል።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ የፋኖ ኃይል "ማኅበረሰቡን በድለዋል፣ ለመንግሥት መረጃ እና ድጋፍ ሰጥተዋል" ብሎ በመጠርጠር የሥራ ኃላፊዎቹን "በየአቅጣጫው አፈላልጎ" በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገለጹ ሲሆን፤ በወረዳው አስተዳደር ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
"ከእስረኞች ውስጥ አንዱ ነበርኩ" ያሉ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የወረዳው የግብርና ባለሙያ በበኩላቸው፤ መስከረም 29 በተደረገባቸው "ጥቆማ" መያዛቸውን ተናግረዋል።
እሳቸውን እና ዘጠኝ ሴቶችን ጨምሮ 115 ሰዎችን በወቅቱ በፋኖ ታጣቂዎች ታስረው እንደነበር ገልጸው፤ "ጠዋት እየገባን ከሰዓት እየመለሱ፤ የሚለቁበት ሁኔታ ነበር" ሲሉ ስለአያያዛቸው ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ በተለይም "በግል ጥላቻ" ታስረው የነበሩ ሰዎችን እያጣሩ መልቀቃቸውን እና 57 ሰዎች መቅረታቸውን ገልጸዋል።
የታጣቂ ሃይሉ መሪዎች እስረኞቹ ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ ማብራሪያ እና ምክር እንደሰጧቸው የጠቆሙት እስረኛው፤ መጨረሻ ላይ እሳቸውን ጨምሮ 37 እስረኞች መቅረታቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሕዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ውጊያ መቀስቀሱን ተከትሎ፤ ሌሊት 9፡00 ሰዓት ላይ ታጣቂ ኃይሎቹ 37ቱን ሰዎች ከታሰሩበት ትምህርት ቤት እንዲወጡ እንዳዘዟቸው ገልጸዋል።
በሥም ዝርዝር በሁለት ቡድን እንደተለዩ እማኝነታቸውን የሰጡት እስረኛው፤ ከፈረስ ቤት ከተማ በግምት ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው 'ፈረስ ቤት ሚካኤል' አካባቢ የሚገኝ ትምህርት ቤት እንደተወሰዱ ተናግረዋል።
በአንደኛው ቡድን 31 እስረኞች፤ በሁለተኛው ቡድን ደግሞ ስድስት እስረኞች በመኪና ተጭነው መወሰዳቸውን አመልክተዋል።
በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር የነበሩት የአካባቢ አመራሮች "ፈረስ ቤት ሚካኤል" በተባለ የከተማው መውጫ ላይ ተወስደው መረሸናቸውን ሦስት ነዋሪዎች እና የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዞኑ ሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ 37 "የፖለቲካ መሪዎች እና የፀጥታ መዋቅሩ አባላት" ለሁለት ወራት ታስረው ገዘንዘብ እንዲከፍሉ እና በማኅበረሰቡ እንዲሸማቀቁ ከተደረጉ በኋላ "በጅምላ ተረሽነዋል" ብለዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ አቶ ዋለ አለማየሁ የወረዳው አስተዳዳሪ፣ ቄስ እንዳለ ገበየሁ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ዘመኑ ይባቤ የእንስሳት ሀብት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ዓይንአለም ስንሻው የውሃ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ወንድይፍራው ጌታነህ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
የሟቾቹን አስከሬን ማኅበረሰቡ ማንሳቱን የጠቆሙ አንድ ነዋሪው፤ በአብዛኛው ቀብር ፈረስ ቤት ከተማ በሚገኙት መድኃኒዓለም እና ገብርኤል በተባሉ አብያተ ክርስቲያናት እና በዙሪያው ባሉ ቀበሌዎች እንደተፈጸመ ገልጸዋል።
የመንግሥት ኃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን ታጥቀው ሕዳር 27/2017 ዓ.ም. ጠዋት 4፡00 አካባቢ ፈረስ ቤት መግባታቸውን የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ መምህር፤ ማኅበረሰቡ በስጋት ከተማዋን ለቆ መውጣቱን ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
አዲሱ የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ የሠራተኞችን መብት የሚጨቁንና ፍትህን ሊያዘገይ የሚችል መሆኑ ተገለጸ
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ባሳለፍነው ወር የፀደቀው አዲሱ የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ የሠራተኞችን መብት የሚጨቁንና ፍትህን ሊያዘገይ የሚችል መሆኑን አሐዱ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
አዲሱ አዋጅ የትኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በተለያየ ምክንያት በመስሪያ ቤቱ የሥራ አመራር ጉባኤ ከሥራ እንዲሰናበት ከተወሰነበት ውሳኔው የመጨረሻ መሆኑን የሚደነግግ ነው።
በተጨማሪም ይህንን ውሳኔ የተቃወመ ሠራተኛ በአስተዳደራዊም ሆነ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች የይግባኝ ቅሬታ የማቅረብ መብት እንደሌለው አዋጁ ይጠቁማል።
አሐዱ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያው አቶ ባየ ጥላሁን እንደገለጹት በሕገ-መንግሥቱ በተቀመጠው መሰረት ከፍርድ ቤት ውጪ በአስተዳደራዊ መልኩ የዳኝነት ሥራን እንዲሰሩ ከተደረጉ አካላት አንዱ ሲቪል ሰርቪስ መሆኑን ጠቅሰው፤ 'ሠራተኛው ከሥራ እንዲሰናበት ከተወሰነበት የመጨረሻው ውሳኔ ይሆናል' የሚለው ግን አዲስ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል።
አዋጁ በአስተዳደራዊ አልያም በመደበኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት ባይቻልም፤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቅሬታ ከማቅረብ የሚከለክል አለመሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም መሰረት የተሰጠው ውሳኔ ሕግን መሰረት ያላደረገና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ካለበት እሱን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚቀርበው አቤቱታ በተፈለገው የጊዜ ገደብና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የሚደረገውን የፍትህ ሂደት ሊያዘገየው እንደሚችል ገልጸው፤ በፍርድ ቤት ቢወሰን የተሻለ እንደሚሆን የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል።
"በሲቪል ሰርቪስ በወንጀል ተጠርጥሮ አስተዳደራዊ ክስ ሲመሰረትበት ሕጉ ምን መደረግ እንዳለበት ያስቀመጠው ነገር ቢኖርም፤ ግን በተግባር ሲውል ገና ጥፋተኛ ከመባሉ በፊት ደሞዝ ማገድ በሀገሪቱ የተለመደ በመሆኑ አቤቱታውን ለበላይ አካል ለማሳወቅ ፍትህ የማግኘት መብቱን በሚጋፋ መልኩ ጫና ያደርግበታል" ሲሉም አክለዋል።
ሌላኛዋ የሕግ ባለሙያ አስናቀች መልካሙ በበኩላቸው "ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት የማይቀርብ ከሆነና ውሳኔው በአስተዳደራዊ ብቻ የሚፀድቅ ከሆነ የሠራተኞችን መብት ይጨቁናል" ያሉ ሲሆን፤ ይግባኝ የማለት መብትንም ሊያስቀር እንደሚችል ገልጸዋል።
በገለልተኛ አካል እንዲታይ እድል ሳይፈጥር በአስተዳደራዊ መልኩ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ከሆነ የህግ ክፍተትን ይፈጥራል ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው አዲሱ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አድርጎ በሦስት ተቃውሞ፣ በአራት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በአማራ ክልል የማዋላጃ ጓንት ጠፍቶ የሕክምና ባለሙያዎች እናቶችን በፌስታል የሚያዋልዱባቸው አካባቢዎች መኖራቸው ተገለጸ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት የመድሃኒቶች አቅርቦት እና የነፍስ አድን ሥራዎች በእጅጉ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ሲል የክልሉ የሲቪል ማህበራት ሕብረት ገልጿል፡፡
እንደ ሕብረቱ ገለጻ ከሆነ በክልሉ ለሕጻናት እና ለእናቶች የሚደረገውን የነፍስ አድን ሥራና ሕክምና፤ የመድሃኒትና የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች እጥረት እየፈተነው በመሆኑ ያለውን ችግር መፍታት ከሁሉም የቅድሚያ ቅድሚያ የሚፈለግ ነው፡፡
"በክልሉ በረሃብ ምክንያት ሕጻናትን ጨምሮ ሰዎች እየሞቱ ነው" ያለው ሕብረቱ፤ ባለሙያዎች እናቶችን ማዋለጃ ጓንት አጥተው በፌስታል የሚያዋልዱባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም ገልጿል፡፡
ክልሉን ትተው ከወጡት 8 አለም ዓቀፍ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውጭ በክልሉ ያሉት ተቋማት ለመንቀሳቀስ እና እርዳታዎችን ለመስጠት ቢሞክሩም፤ ችግሩ ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ የአቅርቦት እጥረት መኖሩን የሕብረቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ደስታ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሳይቀር የእርዳታ ቁሳቁሶችን ይዞ መግባት ይቻላል" ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ "ነገር ግን ከዚህ በፊት የነበረው መጥፎ ልምድ፣ የሲቪል ማሕበራቱን 'ግጭት ካለ እንገባም' እንዲሉ እና ችግሮቹ ትኩረት እንዳያገኙ አድርጓል" ብለዋል፡፡
አቶ ንጋቱ አክለውም በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ለጉዳት እየተዳረጉ እና እየሞቱ ያሉት ጦርነቱን ያላስነሱት ሕጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ "ይህን ጉዳይ ፖለቲካዊ ሽፋን ሰጥቶ ትኩረት መንፈግ የትኛውንም የአለም ዓቀፍ የሰብዓዊ ሕግ አይወክልም" ብለዋል፡፡
ሁሉንም ጉዳይ ፖለቲካዊ ማድረግ አንዱ የሚስተዋል ችግር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ አምራች ገበሬዎች በምግብ እና በሕክምና እጦት ምክንያት እየሞቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"የልማት የእድገትና ሌሎች ሥራዎችን መስራት ቅንጦት ነው" ያለው ሕብረቱ፤ "የነፍስ አድን ሥራዎች በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ያስፈልጋሉ" ሲል ገልጿል።
በዚህም መሠረት "የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመቅረፍ ሊረባረቡበት እና ቢያንስ እናት የምትወልድበት መሰረታዊ አገልገሎት ልታገኝ ይገባል" ብሏል፡፡
በእመቤት ሲሳይ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ቁጠባና ሕብረት ሥራ ማሕበራት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ሊከበር መሆኑ ተገለጸ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የገንዘብ ቁጠባና ሕብረት ሥራ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ76ኛ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ ለማክበር አዲስ አበባ ከተማ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
አዲስ አበባ የገንዘብ ቁጠባና ሕብረት ሥራ ተቋማትን በአግባቡ እየተጠቀመችባቸው ከሚገኙ የፋይናንስ ስርአቶች መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው ተብሏል።
በከተማዋ የሚገኙ ሕብረት ሥራ ማሕበራት አነስተኛ ወለድ ያለው ብድር ለማሕበረሰቡ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን የተገለጸ ሲሆን፤ ከ291 ሺሕ በላይ አባላት ማቀፋቸውን የከተማ አስተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ለአሐዱ በላከው መግለጫ ጠቅሷል።
በአሁኑ ጊዜ ማሕበራቱ የሰበሰቡት አጠቃላይ ካፒታል ከ10 ቢልየን ብር በላይ መድረሱንም የገለጸ ሲሆን፤ በየአመቱ ለተበዳሪዎች ብድር የመስጠት አቅማቸውም በአማካይ ከ2 ነጥብ 7 ቢልየን ብር በላይ መሻገሩን አስታውቋል፡፡
የገንዘብ ቁጠባና ብድር ሕብረት ሥራ ማሕበራት ምጣኔ ሐብቱን በመደገፍ ብሎም የፋይናንስ ተደራሽነት በማስፋፋት ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግሯል።
ዘንድሮ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ሕብረት ሥራ ቀን ነገ በስትያ ታሕሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረው መሆኑንም ቢሮው ለአሐዱ ባለከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሕብረት ሥራ ማሕበራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙ የመጡ የፋይናንስ ተቋማት ሲሆኑ፤ እንደ ሜክሲኮ፣ ታይላንድ፣ ቻይና ሕንድ በመሳሰሉት አገራት በስርዓቱ ከተጠቀሙበት አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
በኢትዮጵያ እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ አገልግሎት እንደልብ እየሰጡ አይጠደሉም የሚል ወቀሳ ሲቀርብባቸው ይስተዋላል።
በአዲስ አበባ ከተማ ያሉት የፋይናንስ ተቋማት ግን ከሁሉም የተሻለ ተደራሽነት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአማኑኤል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ በተደረገ ጥናት በሴቶች ላይ የሚደርሱ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች መቀነሱ ተረጋግጧል ሲል ለአሐዱ ገልጿል።
ዓለም አቀፍ የጸረ- ጾታዊ ጥቃት ቀን ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ "የሴቷ ጥቃት የእኔም ነው ዝም አልልም" በሚል መሪ ቃል ከሕዳር 16 እስከ ታሕሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ለ16 ቀናት ተከብሯል።
አሐዱም "ቀኑን ከማክበር ባሻገር ምን ዘላቂ ሥራዎች ተሰርተው፤ ምን አይነት ውጤት ማግኘት ተችሏል?" ሲል ጠይቋል።
በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ጥቃት ጥበቃና መከላከል ከፍተኛ ባለሙያ ዘካሪያስ ደሳለኝ በምላሻቸው፤ "የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ጉዳይ በመድረክና በአዳራሽ ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚቀር መሆን የለበትም" ብለዋል።
"ለዚህም ክልሎች በየራሳቸው መመሪያዎችን እንዲወስዱና ተግባራዊ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ማስጨባጫ ሥራዎች እንዲሰሩ ይደረጋሉ" ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም በ2008 በተደረገ ጥናት ከ100 ሴቶች 35 የሚሆኑት አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ባስደረገው ጥናት የጥቃት መጠኑ መቀነሱን ገልጸው፤ 20 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።
ጥቃቶችን ለመቀነስ ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በፍትህ ሚኒስቴር በጋራ የሚመራ ብሔራዊ አስተባባሪ አካል የተቋቋመ መሆኑን የጠቆሙም ሲሆን፤ "ብሄራዊ አስተባባሪው በአጠቃላይ ሀገራዊ አቅጣጫዎችን፣ የመፍትሔ ሃሳቦች የሚሰጥና ለየተቋማቱ ኃላፊነት የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
በተጨማሪም በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ወቅት ሥራዎችን የሚሰራ አደረጃጀት መኖሩን የጠቆሙም ሲሆን፤ "ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መከላከል፣ ተጋላጭነት መቀነስና ምላሽ የሚሰጥ መዋቅር ተዘርግቷል" ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በቀጣይ ጥቃት አድርሶ እንደተፈለገ መኖር የማይቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር የገለጹ ሲሆን፤ ጥቃት አድራሾችን መመዝገብ የሚያስችል ዲጂታል የመረጃ ሥርዓት እየጎለበተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ችግሩን ውጤታማ በሆነ መንገድ መከላከል የሚያስችል አስተማሪ ሕግ እየተረቀቀ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ ከሕግ ማሻሻያ ሥራውጎን ለጎን፤ ጥቃት አድራሾችን መመዝገብ የሚያስችል ዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን እየጎለበተ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ጥቃት አድራሾች ጥቃቱን ሲፈጽሙ መረጃቸው ተመዝግቦ ከዲጂታል መታወቂያ ሥርዓቱ ጋር እንዲያያዝ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በክልሎችና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል የሚፈጠር የሻከረ ግንኙነት ለሰላም እጦት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ መምጣቱ ተገለጸ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በክልል መንግሥታትና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል እየተፈጠረ ያለው አለመግባባት በአገረ መንግሥት ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መምጣቱን የሕገ መንግሥትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል አስታውቋል።
ማዕከሉ የመንግሥታት ግንኝነት እንዲጠናከርና የሰላም ጉዳይ ወደ ቀደሞው እንዲመለስ ሁሉም የሚቻለውን ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል።
"በመንግሥታት ግንኙነት አሁናዊ ሁኔታ በተደረገው ጥናት መሰረት፤ የሁለቱ አካላት ተናቦ የመስራቱ ነገር ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ያመላክታል" ሲሉ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለየሱስ ታዬ ለአሐዱ ገልጸዋል።
በማዕከላዊው መንግሥትና በክልሎች መካከል እየተፈጠረ ያለውን አለመግባባት መፈታት፤ ለነገ የማይባል የቤት ሥራ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
ይህ የሻከረ ግንንኙነት በተለይም ፓሊሲዎችን በመተግበር ረገድ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩንም የማዕከሉ ዳይሬክተር ተናግረዋልዋል።
አክለውም፤ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊነትና ዲሞክራሲ አለመዳበር፣ ብዝሃነት ያቀፈ አንድነት በተገቢው አለመዳበር እንዲሁም፤ የመንግሥታት ግንኙነት በተገቢው መልኩ አለመገንባት ህብረ ብሔራዊ የፌደራል ስርዓት እንዳይጠናከር ተግዳሮት እየሆኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ሌላኛው ማዕከሉ እንደ ክፍተት ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል የግጦሽ መሬትና የተፈጥሮ ሐብት ላይ ያሉ ልዩነቶችን ሲሆን፤ ይህም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን እየጎዳው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ችግሩን ለመፍታትም የክልልና የማዕከላዊ መንግሥት ግንኙነት እንዲዳብር በአዋጅ ደረጃ ተደንግጎ ተፈፃሚ የሚሆንበት አሰራር በፌደሬሽን ምክር ቤት መውጣቱ ገልጸዋል።
ይህንኑ ለማጠናከርም የሕገ መንግሥትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል የበኩሉን ደርሻ እየተወጣ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በአማኑኤል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#አሐዱ_ትንታኔ
የእስራኤል እና ሶርያን ስምምነት የጣሱት ኔታንያሁ!
ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/H8Yyiw7Nw94?si=I17UUbo6lI5q5wyk
ከመንግሥት ጋር እርቅ ያወረደው የጃል ሰኚ ቡድን ወደ ምክክሩ እንዲመጣ ተጠየቀ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ ታሕሳስ 7 ጀምሮ እስከ ታሕሳስ 15 ቀን 2017 ድረስ በአዳማ ከተማ በሚያከናውነው በዚህ ውይይት ላይ፤ ከ7 ሺሕ በላይ ተወካዮችን እንደሚጠብቅ የተገለጸ ሲሆን፤ ለዚህ ሥራ የሚሆን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
አሐዱም በቅድመ ዝግጅት ሥራው ላይ ካገኛቸው የኮሚሽኑ የኦሮሚያ ክልል አስተባባሪ ቡድን መሪ ብዙነህ አሰፋ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የቡድን መሪው በአሁን ወቅት በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የሰላም መንገድ ለምክክሩ ጠቃሚ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ "ይህ በሁሉም ቦታ ላይ መተግበር አለበት" ብለዋል።
ከመንግሥት ጋር በትጥቅ ግጭት ላይ ያሉ አካላት ወደ ውይይት እንዲመጡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት አቶ ብዙነህ፤ "ኮሚሽኑ አሁንም ጥሪውን ይቀጥላል" ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ብዙነህ ሀሳባቸውን ሲቀጥሉም በቅርቡም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ የሚጠራው አንዱ ክፍል ከመንግሥት ጋር የሰላም ውይይት ማድረጉን በመግለፅ፤ "ይህ ቡድን ወደ ምክክር መምጣት የሚፈልግ ከሆነ በራችን ክፍት ነው" ብለዋል።
"የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሃሳብ ልዩነት ያላቸው ወገኖች ተገናኝተው የሚወያዩበትን መድረክ ማመቻት እንጂ የእርቅ ሥራ አይሰራም" ሲሉም ለአሐዱ ገልጸዋል።
"ነገር ግን መንግሥት ከታጣቁ አካላት ጋር የሚያደርገው ውይይት መቀጠል አለበት ጥሪውንም ማቋረጥ የለበትም" ያሉ ሲሆን፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት እንዲሳተፉም ከለላ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
አቶ ብዙነህ "አንድ አንድ አማፅያን" ያሏቸው ቡድኖችን ግን "ከመሰረቱ በኮሚሽኑ ዕምነት እንደሌላቸው ሲገልፁ ቆይተዋል፤ ይህንን ግን ኮሚሽኑ ማስገደድ አይችልም" ብለዋል።
የተሞላ ምክክር ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ የገለጹም ሲሆን፤ በአሁን ወቅት በኦሮሚያ ክልል ያለውን አንፃራዊ ሰላም በማፅናት ሌሎች ብረት አንስተው ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
"በመሳሪያ የሚደረገው ፍልሚያ የሚያመጣው ለውጥ የለም" የሚሉት ደግሞ፤ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር ናቸው።
"በቅርቡ በኦሮሚያ የታየው የእርቅ ሂደት በሌሎችም አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትም ወደ ሰላም እንዲመጡ እናበረታታለን" ሲሉ አምባሳደር መሀሙድ ተናግረዋል።
በቅርቡ መንግሥት "ሸኔ" የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው አንዱ ክፍል የሆነውና በጃል ሰኚ የሚመራው ቡድን ከመንግሥት ጋር እርቅ ሰላም ማወረዱ ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለዚህ ቡድን ወደ ምክክሩ እንዲመጣ ጥሪ ተደርጎለታል።
በአቤል ደጀኔ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
አማራ ባንክ አጠቃላይ የሃብት መጠኑ ከ35 ቢሊዮን ብር መብለጡን አስታወቀ
👉 ባንኩ በዛሬዉ ዕለት ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ነው
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አማራ ባንክ የባለአክሲዮኖች 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በዛሬው ዕለት በማካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በጉባዔው ላይም አጠቃላይ የሃብት መጠኑ 35 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታዉቋል።
ባንኩ የብድር የቅድሚያ ክፍያውን በ33 በመቶ በማሳደግ 20 ቢሊዮን ብር አካባቢ ማድረሱን የገለጸ ሲሆን፤ የመደበኛ እና የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አጠቃላይ ተቀማጭ በ26 በመቶ ጨምሮ ወደ 25 ቢሊዮን ብር ማደጉንም ገልጿል።
በተጨማሪም የዓመቱ አጠቃላይ ገቢ 146 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን የገለጸው ባንኩ፤ በዚህም 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጿል።
ባንኩ ሰፊውን የማህብረሰብ ክፍል ለማገልገል አልሞበት የተነሳበትን ራዕይና 'ከባንክ ባሻገር' የሚለውን መሪ ቃሉን እውን ለማድረግ፤ ከፍተኛ የሃብት መጠን ለማካበት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የቦርዱ ሰብሳቢዎች በጉባዔው ተናግረዋል።
ከተደራሽነት አንፃር ባደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ 143 ተጨማሪ ቅርጫፎችን በመላ ሀገሪቱ በመክፈት፤ በአሁኑ ወቅት የቅርጫፎቹን ብዛት 310 ማድረሱንም አስታዉቋል።
በተጨማሪ የባንኩ የደንበኞች ብዛት ከ1 ነጥብ 8ሚሊዮን በላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ 600 ሺሕ የሚጠጋ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ገልጿል።
ባንኩ "በባለፉት ዓመት የገጠመዉን ኪሳራ በፍጥነት በማካካስ ካለፈዉ ዓመት ካገኘዉ ትርፍ ጋር ሲነፃፀር፤ የዘንድሮው ከ669 ሚሊዮን ብር ልዩነት አሳይቷል" ብሏል።
በደረጄ መንግስቱ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#አሐዱ_አንቀፅ
"ብሄር እንጂ ሃገር የሚል ዜጋ ተመናምኗል"
ሙሉ ጥንቅሩን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/glkA-Ni1QVQ?si=WB0r7CVR1cSJ_C-V
ዘጠኝ ተቋማት አውሮፕላን ማረፊያንና ድንበርን በተቀናጀ መልኩ ለማስተዳደር የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ተገለጸ
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አውሮፕላን ማረፊያን እና ድንበርን በተቀናጀ መልኩ ለማስተዳደር የሚያስችል ስምምነት በዘጠኝ ተቋማት መካከል መፈረሙ ተገልጿል።
ይህም ስምምነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እና አገልግሎቱን ለማዘመን የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
በዚህም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች የሚኖራቸውን ቆይታ እንዲያራዝሙ፣ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበትን መንገድ ማቅለልና አስተማማኝ ደህንነት እንዲኖር ለማስቻል ስምምነቱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ስምምነቱን ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለመሆናቸው ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#አሐዱ_ትንታኔ
"አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሾመችው ሶርያ"
ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/N9Po_D0hE98?si=zV7-aGwC4BUdtBfn
በደቡብ ኦሞ ዞን ሕጻናትን በጫካና ገደል ውስጥ በመጣል ለህልፈት የሚዳርገው 'ሚንጊ' ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አሁንም መቀጠሉ ተነገረ
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ሕጻናትን በጫካና ገደል ውስጥ በመጣል ለህልፈት የሚዳርገው 'ሚንጊ' የተሰኘው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አሁንም መቀጠሉን የወረዳው ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ አስታውቋል።
ጎጂ ድርጊቱ በሁለት ወረዳዎች የቆመ ይሁን እንጂ፤ አሁንም ድረስ በ22 ቀበሌዎች እየተፈፀመ በመሆኑ ሕጻናት ለሞት እየተዳረገ ይገኛል ብሏል።
በተለይም በወረዳው ከሚገኙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል 'ሚንጊ' አስከፊው መሆኑም ተነግሯል።
በዚህም የተነሳ 'የሕጻናቱ የላይኛው ጥርስ ቀድሞ ከበቀለ ለቤተሰብም ሆነ ለማህበረሰቡ ድርቅ የሚያስከትል እና መጥፎ ዕድል የሚጠራ ነው' በሚል ሕጻናት እንደሚገደሉ፤ በወረዳው ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ የሴቶችና ሕጻናት መብት ደህንነት ቡድን መሪ ወይዘሮ ሙሉነሽ ጨረና ለአሐዱ ተናግረዋል።
በተጨማሪም አንድ ለትዳር የደረሰች ሴት ከጋብቻ በፊት ቀድማ ካረገዘች እንዲሁም፤ አግብታ የመጀመሪያ ልጅ ከወለደች በኋለ ሽማግሌዎችን ያሳተፈ የባህል ደንብን የተከተለ ዝግጅት ተደርጎ ሳትመረቅ ሁለተኛ እርግዝና ከተፈጠረ ሕጻኑ እንዲሞት የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን አክለዋል።
"ግንዛቤ በተፈጠረላቸው ቀበሌዎች ልጃች ከሚገደሉ የአደራ ቤተሰብን ጨምሮ 'በሌሎች አካላት ይደጉ' በሚል ፈቃደኛ ሆነው የሚሰጡ ወላጆች በመኖራቸው፤ 83 ሕጻናት በጥሩ ሁኔታ እያደጉ ነው" ብለዋል።
"ነገር ግን ችግሩ አሁንም ድረስ የዘለቀ ነው" የሚሉት ወይዘሮ ሙሉነሽ፤ በቅርብ ወራቶች ብቻ በአምስት ሕጻናት ላይ ድርጊቱ ተከስቶ በቤተሰብ እና በአደራ ተሰጥተው እያደጉ መሆኑንም ለአሐዱ ተናግረዋል።
ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል የተባለ ሲሆን፤ "የተፈጠረውን ግንዛቤ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻል እንቅፋት ሆኗል" ተብሏል።
"በተለይም ችግሩ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል ከመሆኑ አንፃር ፈታኝ ነው" ያሉት ወይዘሮ ሙሉነሽ፤ የማህበረሰብ ውይይት ያልተዳረሰባቸው ቀበሌዎች መኖራቸውና የተደራሽነት ውስንነት መኖር ችግሩን ለመቅረፍ ተግዳሮት እየሆነ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በአበረ ስሜነህ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በመዲናዋ የሥነ ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 29 የደንብ ማስከበር ሠራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሥነ ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 29 የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ሠራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለአሐዱ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከደንብ አስከባሪዎች ጋር ተያይዞ የሥነ ምግባር ችግሮች እንዳሉ ቅሬታ ሲነሳ ይሰማል፡፡
ለአብነትም በአዲስ አበባ በንግድ ስራና የሕንፃ ባለሙያዎች "እንዳንሰራ የደንብ አስከባሪዎች ተፅዕኖ እያደረጉብን ነው" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አክለውም "የደንብ ልብስም ያለበሱ 'ደንቦች ነን' በሚል ንብረት እየወረሱ ይወስዳሉ" በማለት ቅሬታቸዉን ለአሐዱ አሰምተዋል፡፡
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን 'ሕገ ወጥ እቃ ይዛችኋል' በሚል ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸሙባቸዉ መሆኑን እንዲሁም፤ የግንባታ ፍቃድ አውጥተዉ እየሰሩ ቢሆንም ካለአግባብ ገንዘብ እየተጠየቁ መሆኑንም ገልጸዋል።
አሐዱም "የደንብ ማስከበር ባለሙያዎች 'ደንቦች ነን' በሚል ገንዘብ ተቀብሎ ንብረት ወርሶ የመሄድና በድጋሚ ከአንድ ሳምንት በኋላ ተመልሶ ገንዘብ መጠየቅ ይስተዋል፤ ይህ አግባብ ነው ወይ? ተጠያቂነቱስ እስከምን ድረስ ነው?" ሲል ጠይቋል፡፡
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ የምስራች ግርማ ችግሩ በሰጡት ምላሽ፤ "ችግሩ አይኖርም ማለት አይቻልም" ያሉ ሲሆን፤ "መሰል ችግሮችን ማህበረሰቡ ሲመለከት ጥቆማ ሊሰጠን ይገባል" ብለዋል።
ጥቆማ መስጠቱ እንዳለ ሆኖ በሚደረግ ክትትል ባለስልጣኑ በሩብ ዓመቱ የተለያየ የሥነ ምግባር ጥሰት ፈፅመዋል ያላቸው 29 ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ደሞዝ ቅጣት የደረሰ የእርምት እርምጃ ተወስዷል ሲሉ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ የምስራች ግርማ ለአሐዱ ተናግረዋል።
የደንብ ልብስ ያለበሱ ደንቦችን በሚመለከት የደንብ ባለስልጣን በጎ ፈቃደኞች መኖራቸዉን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ "ከአቅም በላይ ሲሆን የወረዳ አመራር እና ሀላፊዎች የደንብ ማስከበር ሥራ ያግዙናል" ሲሉ ገልጸዋል።
በህይወት ጌትነት
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ከ1 ሚሊየን በላይ ሕጻናት ክትባት ያልወሰዱ ቢሆንም አሁንም ክትባቱ እንዳይሰጥ ጫና እንደሚደረግበት የጤና ሚኒስቴር ገለጸ
ታሕሳስ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከ1 ሚሊየን በላይ ሕጻናት ክትባት አለመውሰዳቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እነዚህ ሕጻናት የክትባት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ከመደበኛው የክትባት ፕሮግራም በተጨማሪ በዘመቻ መልክ እየተሰጠ መሆኑንም መገለጹ ይታወቃል።
ነገር ግን እነዚህን ሥራዎች በመስራት ሂደት ውስጥ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ክትባት እንዳይሰጥ በተለያየ መንገድ የግጭቱ ተሳታፊዎች ጫና እያደረጉበት መሆኑን የገለጹት፤ በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ናቸው።
ሚኒስትር ደኤታው "ይህን ችግር ለመፍታት የጤና ሚኒስቴር መድረስ የማይቻልባቸው አካባቢዎችን በግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደ ቀይ መስቀል ያሉ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ክትባት የመስጠት ሥራዎች እየተስሩ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።
ምንም አይነት ክትባት ካልወሰዱ ሕጻናት በዘመቻ መልክ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕጻናትን መድረስ መቻሉን አንስተዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ክትባት ጀምረው ያቆሙ ሕጻናት ቁጥር 1 ነጥብ 7 ሚሊየን መሆኑን መገለጹ ይታወሳል።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#ADVERTISMENT
#ጊፍትሪልስቴት
ታላቅ የምስራች!
**
ጊፍት ሪል ስቴት ከ10% ቅድመ ክፍያ ጀምሮ በ22 ሳይቶቹ ቅንጡ አፓርትመንቶችን እና የንግድ ሱቆችን ለሽያጭ አቅርቧል፡፡
ይህ ሳይት ለአፓርትመንትና ንግድ ሱቆች የሚውሉ G+25 ሶስት መንታ ህንጻዎች ያሉት ሲሆን የዚህ 6ኛ መንደር መለያዎች፡-
•ከባለአንድ እስከ ባለአራት መኝታ ክፍሎች ያሉት፣
•ለመኖሪያም ሆነ ለንግድ ተመራጭ አካባቢ የሆነ፣
•በአንድ ወለል ሶስት ቤቶች ብቻ ያሉት፣
•በእያንዳንዱ ወለል ስድስት አሳንስር ያለው፣
•አራት ቤዝመንት ያሉት በቂ የመኪና ማቆሚያ የተዘጋጀለት፣
•24 ሰዓት የኤሌክትሪክ፣ ኢንተርኔትና ውሃ አቅርቦት አሉት፣
ጊፍት ሪል ስቴት
ማህበረሰብን እንገነባለን!
ለበለጠ መረጃ፡-
Website: https://www.giftbusinessgroup.com
Twitter: https://twitter.com/GIFTBusinessG
YouTube: www.youtube.com/channel/UCcqr7cpVv9ski-F7haxXx4w
Facebook: www.facebook.com/profile.php?id=100090918391017...
Telegram: /channel/giftbusinessgroup
Short Code: 8055
#አሐዱ_ለዛና_ቁምነገር
"ከ21ኛ ክፍለ ዘመን ታምራት አንዱ የአሳድ በስልጣን መቆየት ነው" በአለምነህ ዋሴ
ሙሉ ጥንቅሩን ለመከታተል ከሥር ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ!
👇
https://youtu.be/wkKGfaDUkTA?si=goCEa6ud_z5ha0g6
ምርጫ ቦርድ የአምስት ፓርቲዎችን እግድ አነሳ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠቅላላ ጉባዔ፣ ከኦዲትና በሴት አባላት ቁጥር አማካኝነት ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ጋር በተገናኘ 11 ፓርቲዎች ላይ የዕግድ ውሣኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ቦርዱ ከታገዱት ፓርቲዎች ውስጥ የይቅርታና የመከላከያ መልስ ያቀረቡትን አምስት ፓርቲዎች፤ ማለትም የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎ.ብ.ን)፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አ.ት.ፓ)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋ.ህ.ዴ.ን)፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት (ኢ.ዴ.ህ) እና የአገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጉዳይን መርምሮ፤ ፓርቲዎቹ ያለፈውን ስህተት እንደማይደግሙና በቀጣይም በሚያቀርቧቸው መረጃዎች ጥራት በመተማመን እግዱን ማንሳቱን ገልጿል።
እግዱን ለማንሳት የቦርዱን ሥራ ከሚያደናቅፍና ዕምነትን ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱ ተግባራት ተቆጥበው፤ በሕግ አግባብ ብቻ እንደሚንቀሳቀሱ በማመን መሆኑንም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
አሐዱ በወቅቱ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለእግዱ "መረጃዎችን ዲጂታላይዝድ አድርጎ ከማቅረቡ አንጻር ያለን ልምድ እና ግብዓት አነስተኛ በመሆኑ፤ የጠየቀውን መረጃ ማስገባት ባለመቻላችን ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
እንዲሁም "ቦርዱ የነበረውን ተግዳሮት መገንዘብ አቅቶት ሳይሆን፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለመቀነስ የሚመስል ነገር አለው" በማለት ትችት አቅርበው ነበር።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
#አሐዱ_አሳሩ_በዛብህ
"ሹመትን ከገንዘብ ጋር ያያዘው የመዲናዋ ፌደሬሽን"
አሳሩ በዛብህ በሳምንቱ አሳሰበኝ ያለውን ጉዳይ በብዕሩ ከትቦ፤ ለወዳጁ ምክረ ሰናይ ልኮለታል፡፡
ሙሉ ጥንቅሩን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/elKfGWE6LYs?si=ZiWd4SPAU5bpq7WE
አማራ ባንክ አዳዲስ ፈጠራዎችን እና ዘላቂ እድገትን በቀጣይ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቀ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አማራ ባንክ ቀጣይ የእድገት ጉዞዎቹን እውን ለማድረግ፤ የዲጂታል ሽግግርን የማስፋፋት እንዲሁም የፋይናስ ተደራሽነትን የማረጋገጥ ተልዕኮዎችን እንደሚያስፈፅም የባንኩ የዳይክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ከበደ አስታዉቀዋል።
በተለይም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲሁም በልማት ሥራዎቹ ላይ ትኩረት በመስጠት እና ምቹ እድሎቹን በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ እድገቱን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል፡፡
"የቁጥጥር ልቀትን ማጠናከር እና ታማኝነት የሥራችን ምሰሶ ነው" ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ "አሰራራችን ሥነ ምግባርና ግልፀኝነት የተሞላበት መሆኑን ለማሳየት ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ ያለዉን ሥራ አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነን" ሲሉ በዛሬዉ ዕለት በተካሄደው የባንኩ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ቃል ገብተዋል።
በተጨማሪም ባንኩ ከወለድ ነፃ አገልግሎቱን በማስፋት የማህበረሰቡን ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ አዳዲስ የወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎቶችን እና ቅርጫፎችን ለማስፋት ተመሳሳይ ተልዕኮ ካላቸዉ ድርጅቶች ጋር አጋርነትን በመፍጠር መስራት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።
በጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት እና በፋይናስ አካተችነት እየሰራ የሚገኘው ባንኩ፤ የለውጥ ግቦችን ለማሳካት የዕለት ተእለት የሥራ ክንዉኑ መሆኑንም የቦርዱ ሰብሳቢው ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚያ ማሻሻያ ማድረጓን ተከትሎ የባንኩ ዘርፍ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን የገለጹት ሰብሳቢው፤ ባንኩን የውጭ ምንዛሪ እጥረቶች እና የፀጥታ ችግር እየፈተኑት እንደሚገኝም ገልጸዋል። "ነገር ግን ምንም እንኳን ፈታኝ ተግዳሮት ቢገጥሙት ባንኩ ተወዳዳሪነቱ የማይበገረ ነው" ብለዋል።
ባንኩ የበጀት ዓመት የገበያ ተለዋዋጭነትን፣ የማክሮ ኢኮኖሚይ ሁኔታዎችን እና የወደፊት የእድገት አቅምን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ የቀጣይ አምስት ዓመት ማለትም ከ2024 እስከ 2029 ስትራቴጅካዊ ፍኖታ ካርታ መንደፉን አስታውቋል።
በዚህ ዓመት የዲጂታል ብድር እና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልእሎትን ጨምሮ አዳዲስ ምርቶችን በመልቀቅና ተደራሽነቱን በማስፋት የደንበኞቹን አቅም ከፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።
በዘንድሮዉ ዓመት ባንኩ ቅድሚያ ከሚሰጣቸዉ የጥረት አገልግሎቶች ውስጥ የደንበኞችን አገልግሎት ማሻሻል ቅዳሚው መሆኑም ተጠቁሟል።
በደረጄ መንግስቱ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ አገልግሎት በመድሃኒት መደብሮች እንዲሰጥ በእቅድ መያዙ ተገለጸ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የመድሃኒት መሸጫ መደብሮች የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ አገልግሎት እና የክትባት የአገልግሎት የሚሰጡበት አሰራር እንዲኖር ለማስቻል በእቅድ መያዙን የኢትዮጵያ የመድሀኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማህበር አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋክቶላ መድሃኒት መደብሮች መድሃኒቶችን ከመሸጥ አገልግሎት በተጨማሪ በድንገት ለሚያጋጥሙ እና ለተጨማሪ ለሚያስፈልጉ አገልግልቶች የመጀመሪያ ሕክምናን እርዳታን እንዲሰጡ ለማስቻል መታሰቡን ተናግረዋል።
አገልግሎቱን ከመስጠቱ በፊት በዘርፉ የተመረቁ ባለሙያዎችን በማሰልጠን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በእቅድ ስለመያዙም ገልጸዋል፡፡
የመድሃኒት መደብሮች በሀገሪቱ በቅርበት የሚገኙ ከመሆኑ አንጻር ዜጎች የሕክምና አገልግሎቱን በአፋጣኝ እና በቅርባቸው እንዲያገኙና የጤና ተደራሽነትን ምቹ ለማድረግ ያስችላል ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በሌሎች ባደጉ ሀገራት መሰል አገልግሎቶች በመድሃት መደብሮች አማካኝነት የሚሰጥበት አሰራር ስለመኖሩ የተናገሩት የማህበሩ ፕሬዝደንት፤ የመጀመሪያ እርዳታን በመድሃኒት መደብሮች አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ማህበሩ በቀጣይ ለማከናወን ካቀዳቸው ዘጠኝ የትኩረት አቅጣጫ ውስጥ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
አሜሪካ በግዛቷ ለሚወለዱ ሕጻናት ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅደውን ሕግ ልትሽር ነው
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሀገሪቱ ለሚወለዱ ሕጻናት ዜግነት እንዲሰጣቸው የሚፈቅደውን ሕግ እንደሚሰርዙ ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የከረረ አቋም እንዳላቸው በተደጋጋሚ የተናገሩ ሲሆን፤ ሕገ ወጥ ስደተኞችንም በሀይል እንደሚያባርሩ ተናግረዋል፡፡
አሁን ደግሞ "በአሜሪካ ለሚወለዱ ሕጻናት ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅደውን ሕግ እሽራለሁ" ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ በግዛቷ የሚወለዱ ሕጻናት በቀጥታ የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅድ ሕግ ያላት ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በርካታ ዜጎች በአሜሪካ ለመውለድ አስቀድመው ወደ ስፍራው ያቀናሉ፡፡
"ስደተኞች የአሜሪካዊያንን ጥቅም እየጎዱ ነው" የሚል አቋም ያላቸው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ "ይህን ሕግ እሰርዛለሁ፣ አሜሪካዊ ልጆች ያሏቸውንም ወላጆች አብሬ ወደመጡበት አባርራለሁ" ሲሉም መዛታቸውን አል አይን ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ አምስት ሚሊዮን ዜጎች አሜሪካዊ ካልሆነ ስደተኛ ዜጎች የተወለዱ ሲሆን፤ የዶናልድ ትራምፕ መመረጥን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች የመባረር ስጋት ውስጥ ናቸው፡፡
አሜሪካ ከአንድ ወር በፊት ባካሄደችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን መምረጧ የሚታወስ ሲሆን፤ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጥር አጋማሽ ላይ ስልጣን እንደሚይዙ ይጠበቃል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
በኦሮሚያ ክልል የመሬት አስተዳደር ሕጉን ባለማወቅ በገጠር መሬቶች ላይ የተገነቡ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑ ተገለጸ
ታሕሳስ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል የመሬት አስተዳደር ሕጉን ባለማወቅ ምክንያት፤ በገጠር መሬቶች ላይ ቤቶችን የገነቡ ግለሰቦች ቤታቸው እንዲፈርስ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር ለአሐዱ ገልጿል።
አስተዳደሩ "አብዛኛው ህብረተሰብ በገጠር መሬት ላይ መኖሪያ ቤት ለመስራትም ሆነ ሌሎች ተግባራትን ለመፈጸም ሕጋዊ አካሄድ መኖሩን ግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባቱ ምክንያት በርካታ ዜጎች በኦሮሚያ እና ዙሪያው የገነቡት ቤት እንዲፈርስባቸው ተደርጓል" ብሏል።
በኦሮሚያ ገጠር መሬት አስተዳደር ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ መላኩ ፉርጋሳ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ "አርሶ አደሩም ቢሆን በመሬቱ ላይ ቤት ለመስራት ሲፈልግ በቅድሚያ ሕጋዊን አካሄድ ማሟላት ይጠበቅበታል" ብለዋል።
በዚህም የገጠር የእርሻ ወይንም ሌላ አይነት መሬት ላይ ተገንብቶ የተገኘ ቤት የሚፈርስ መሆኑን አንስተዋል።
አሐዱም "በኦሮሚያ ዙሪያ በተደጋጋሚ ለሚስተዋለው የዜጎች መኖሪያ ቤት ፈረሳ ምክንያት የዚህ ሕግ መኖር ነው? ወይ ሲል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ ባለሙያውም "እንደየ አካባቢው መዋቅራዊ አሰራር የሚለያይ ቢሆንም በሕገወጥ መንገድ የተፈጸመ ግብይት ከሆነ ግን እርምጃ የሚወሰድበት አግባብ አለ" ብለዋል።
"የገጠር መሬት አገልግሎቱ ለግብርና ነው" ያሉት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው፤ "ለመኖሪያነት አገልግሎት መስጠት ያለበት የከተማ መሬት ነው" ብለዋል።
ይህ ሕግ ባይቀመጥ ኖሮ ሁሉም የግብርና መሬቶች ወደ መኖሪያነት ሊቀየሩ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ ስለ አዋጁ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ለአስተዳደር ሠራተኞችና ለባለሙያዎች ስልጠናዎችን እንደሚሰጡ ገልጸው፤ "ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ግን በጥናት የሚለይ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 248/2015 መሻሻሉ ይታወቃል።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ኮሚሽኑ ሁሉም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲተገበር መጠየቁ ትክክለኛ ነው ሲል ገለጸ
ሕዳር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን በመመለስ ሂደት ውስጥ ሁሉም የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መፈፀም እንደሚገባው መጠየቁ ትክክለኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዐቢይ ኮሚቴ በማቋቋም ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የገለጹት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ተስፋዓለም ይህደጎ፤ የቀድሞ ተዋጊዎች በተለይም በግብርና፣ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም በተለያዩ ሥራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ተግባር መጀመሩን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከተለያዩ ተቋማትና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች 'ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመመለሱ ሥራ ግልፅ አይደለም' ተብሎ የሚነሳው ጉዳይ፤ ኮሚሽኑ ግልፅ ነው ብሎ እንደማያምን ገልጸዋል፡፡
ይህ የተሃድሶ ሥራ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንድ አካል መሆኑን ያነሱት አቶ ተስፋዓለም፤ "ይህም ተፈፃሚ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል።
በተለይም የተፈናቃዮች ጉዳይ እና የሌሎች ሀገራት ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል ያለመውጣት የመሳሰሉት ጉዳዮች ተፈፃሚነታቸው ላይ ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡
"በስምምነቱ መሰረት የፌደራል መንግሥት እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ በመነጋር በመጠለያ ጣቢያ ያሉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እንዲሰራ ጥሪ እያቀረብን እንገኛለን" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አክለውም "የቀድሞ ታጣቂዎችን መመለሱ እንዳለ ሆኖ፤ ሌሎች የስምምነቱ ውሎች እንዲፈፀሙ መጠየቅ ይገባል። አግባብ ነውም" ብለዋል፡፡
ከፌደራል መንግሥት ጋርም ቀጣይነት ያለው ንግግር በማድረግ በጊዜያዊ አስተዳደሩና የፌደራል መንግሥቱ መካከል መተማመን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
" 'የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመመለሱ ስራ ተገቢ አይደለም' የሚል ፓርቲም ይሁን ሌላ አካል ቆም ብሎ ማሰብ አለበት" ሲሉም አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በክልሉ የተጀመረው የተሃድሶ ሥራ በበጎ ጎኑ የሚነሳ መሆኑን ቢያነሱም፤ ነገር ግን ሁሉም የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነቶች መተግበር አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተለይም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሰፋፊ ቦታ በሌሎች ሃይሎች ቁጥጥር ሥር መሆኑ ጥርጣሬ እየፈጠረባቸው መሆኑንም ለአሐዱ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግሥት ባሳለፍነው ሳምንት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባደረገው ውይይት፤ በተለይም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው የሚመለሱበትን ሁኔታና ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ ሂደት በትኩረት የሚሰራበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት መደረሱን ገልጿል፡፡
በአቤል ደጀኔ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ