አሐዱ ራድዮ 94.3 Your source for top local and international news and analysis. "Voice of Ethiopian" የአሐዱ የቴሌግራም ቻናል ቤተሰብ በመሆን ወቅታዊና እውነተኛ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ
ኤርትራን ከኢትዮጵያ የሚያዋስነው ድንበር ክፍት መሆኑ አሳሳቢ ነው ተባለ
መስከረም 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኤርትራ ሰራዊት አባላት በብዛት የሚገኙበትና ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስነው ድንበር ክፍት መደረጉ አሳሳቢ ነው ሲል ኢሮብ አኒና የተሰኘ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅት ገለጸ፡፡
በአብዛኛው ማለት በሚቻል ሁኔታ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በምትዋሰንበት አካባቢዎች ያሉት ቦታዎች ምንም አይነት የድንበር ጠባቂ እንደሌላቸው ተገልጿል፡፡
የኤርትራ ሰራዊት አባላት በአካባቢው የሚገኙ ወረዳዎችን ከመቆጣጠር ባለፈ፤ መታወቂያ እያሰሩ "የኤርትራዊ ዜጋ ናቹሁ" በማለት በጉልበት ነዋሪዎቹን እያስገደዱ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
ይህንን በሚመለከት የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአሐዱ አሰምተዋል።
በዚህ ረገድ "በዛላንበሳ የነበሩ ከ50 የማይበልጡ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ቦታውን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ፤ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ያለው ቦታ ክፍት ሆኗል" ሲሉ ኢሮብ አኒና የተባለ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅት የቦርድ አባል አቶ ተስፋይ አውዓላ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"መንገዱን በመዝጋቱ የተነሳ ምንም ዓይነት እርዳታ ወደ አካባቢው ማድረስ ባለመቻሉ፤ ማህበረሰቡ ለከፍተኛ ቀውስ እየተዳረገ ነው" ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከዛ ባለፈም "ነዋሪዎቹ በግዴታ 'ኤርትራዊ ናችሁ' እየተባሉ እየተገደዱ ነው" ሲሉም አንስተዋል፡፡
ከሰሞኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በሰጡት መግለጫ፤ "አሁን ላይ የኤርትራ ሰራዊት በተጨማሪነት የያዘው መሬት የለም" ሲሉ መግለጹ አይዘነጋም።
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በባህር ዳር የሚገኙ 24 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ አለመጀመራቸዉ ተገለጸ
መስከረም 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ 24 ትምህርት ቤቶች እስካአሁን የመማር ማስተማር ሥራ አለመጀመራቸዉን የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሙሉአለም አቤ፤ አሁን ላይ መሀል ከተማ ላይ ያሉት ትምህርት ቤቶች ብቻ ትምህርት መጀመራቸዉን ገልጸው፤ ነገር ግን 4 የሁለተኛ ደረጃ እና 20 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በድምሩ 24 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ትምህርት አለመጀመራቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አክለውም፤ ተማሪዎች ትምህርት ወደተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ሄደዉ እንዲመዘገቡ መመሪያ ቢሰጥም፤ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ፍቃደኛ አለመሆናቸዉን አንስተዋል።
በሌሎች የገጠር ከተሞች ያለው የትምህርት እንቅስቃሴም የተለያየ ፈተና ውስጥ በመግባቱ ወደ ትምህርት ገበታ የሚመጡ ተማሪዎች አለመኖራቸውን ዶክተር ሙሉአለም አስረድተዋል።
በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች ምክንያት፤ በተለይም በገጠራማው አካባቢዎች እስካሁን ትምህርት አለመጀመሩ እየተገለጸ ይገኛል።
በእመቤት ሲሳይ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ኢሰመኮ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የግጭት ተሳታፊ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ በድጋሚ ጠየቀ
👉መስከረም 6 በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ከተካሄደው የትጥቅ ግጭት ቢያንስ 20 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል
መስከረም 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በድጋሚ ጠይቋል።
ኮሚሽኑ የግጭቱ ተሳታፊዎች፤ በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፣ በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ አሳስቧል፡፡
እንዲሁም በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፤ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ ጠይቋል።
ኢሰመኮ ይህን ያለው በኢትዮጵያ የበጀት ዓመት አቆጣጠር መሠረት ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ያለውን ጊዜ በሚመለከት ባወጣው የሩብ ዓመት ሪፖርት ላይ ነው፡፡
በሪፖርቱ በተለይ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብት ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል መበራከታቸውን አመላክቷል።
እነዚህ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢ ሆነው የቀጠሉ ጉዳዮች፤ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በአማራ ክልል በስፋት እየተፈጸሙ እንደሚገኙም አንስቷል፡፡
እንደ አብነትም በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ደባርቅ ከተማ መስከረም 6 ቀን 2017 በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጣቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል፤ ከጠዋት እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከተካሄደው የትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ፤ ዒላማቸውን ባልጠበቁ ተኩሶች እና በተባራሪ ጥይቶች ቢያንስ 20 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ የከተማው ነዋሪዎች እና የዐይን ምስክሮች ማስረዳታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በተጨማሪም 9 ሰዎች ደግሞ ከቤታቸው እየተወሰዱ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እንደተገደሉ ነዋሪዎች መናገራቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ከገጠር ወደ ደባርቅ ከተማ መጥተው አልጋ ይዘው የነበሩ 5 መምህራን ይገኙበታል ብሏል።
እንዲሁም ዒላማቸውን ባልጠበቁ ተኩሶች እና በተባራሪ ጥይቶች 36 ሲቪል ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ደባርቅ አጠቃላይ ሆስፒታል ገብተው የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንድ የ3 ዓመት ሕፃንን ጨምሮ 2 ሰዎች እንደሞቱ ለማወቅ መቻሉንም አስታውቋል።
በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ከላይ በተጠቀሱ 5 ክልሎች ላይ ባለፉት ሦስት ወራት ተፈጽመዋል ስላላቸው ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ በዝርዝር በሪፖርቱ አካቷል፡፡
ስለሆነም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምና በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከቀጠሉ የትጥቅ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ይፋ ባደረጋቸው መግለጫዎችና የክትትል ሪፖርቶች የተካተቱና በከፊል ወይም በሙሉ ተፈጻሚ ያልሆኑ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡
መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ በሚገኙት የትጥቅ ግጭቶች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎችን እና አባላትን እንዲሁም የታጣቂ ቡድኖች አባላት ተጠያቂ ለማድረግ፤ ተአማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመርም አሳስቧል፡፡
በግጭቶቹ በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በንብረት ላይ ያደረሱትን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲያደርግም ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች እንዲሁም በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ጉዳያቸው በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት እንዲታይ አሳስቧል፡፡
የመንግሥት የጸጥታና የአስተዳደር አካላት በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ግለሰቦችን በመደበኛ ማቆያዎች ብቻ እንዲይዙና የተያዙ ሰዎች ያሉበት ቦታና ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው እንዲገለጽም ጠይቋል፡፡
መንግሥት በጸጥታ አካላት አባላት፣ በታጠቁ ቡድኖች እና በ3ኛ ወገኖች የሚፈጸሙ እገታዎችን ለመከላከል እንዲሁም የአጥፊዎችን ተጠያቂነት እና የተጎጂዎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ውጤታማ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባልም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስገድዶ መሰወረንና ሰዎች ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ አስሮ ማቆየትን በሚመለከት ራሱን የቻለ ዝርዝር መግለጫ ይፋ እንደሚያደርግም በሪፖርቱ ገልጿል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን ውጥረት እንዲያረግብ ተጠየቀ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን በቀይ ባሕር አካባቢ እየተስተዋለ ያለውን ውጥረት እንዲረግብ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ተጠይቋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያን ጨምሮ ሱማሊያና ግብፅ እየተስተዋለ ያለውን መገዳደር፤ በአፍሪካ አገራት መካከል ባለው የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መምጣቱን ተገልጿል።
ይህ የተነገረው በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ አፍሪካ ሕብረት አዳራሽ በተጀመረው የፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው።
በአገራቱ እየተስተዋለ ያለውን ውጥረት አምራች ኢንዱስትሪዎችና በንግድ ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መምጣቱን በስብሰባው ላይ ሲነገር ሰምተናል።
በዚህ የተነሳም በአገራት መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ በእጅጉን እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ተገልጿል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ሊሰናከል ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው አፍሪካውያን የምጣኔ ሐብት አንቀሳቃሾች ሲናገሩ ሰምተናል።
በቀይባሕር ሲደረግ የነበረው የንግድ ልውውጥ ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱንም ተነግሯል።
ለዚህም የሚመለከተው ሁሉ የመፍትሔው አካል እንዲሆን በጉባዔው ተጠይቋል።
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ለብዙሃን ትራንስፖርት የሚውሉ አውቶቢሶች ግዥ ሊፈፅም መሆኑን ተገለጸ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ እየተስተዋለ ያለውን የሕዝብ ትራንስፖርት ማመላለሻ ችግር ለመቅረፍ የአዳዲስ አውቶቢሶች ግዥን ጨምሮ ብልሽት የገጠማቸውን አውቶብሶች ለመጠገን በጀት መያዙን የአዲስአበባ ትራንስፓርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዳኛቸው ሽፈራው ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳድሩ በከተማዋ እየተስተዋለ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ በጀት እንደተመደበ ነግረውናል።
ምክትል ኃላፊው በአለም አቀፍ ያለውን የነዳጅ እጥረትን ጨምሮ የዋጋ ንረትም ለመቆጣጠር የብዙሐን ትራንስፖርትን መጠቀም የከተማ አስተዳድሩ አስፈላጊ ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጸው፤ "ሕብረተሰቡም መንግሥት ያቀረበውን አማራጭ ሐሳብ በአግባቡ እንዲረዳ ያስፈልጋል" ብለዋል።
አክለውም፤ የከተማ አስተዳድሩ ለትራንስፖርት ዘርፉ እያደረገው ያለው ድጎማ ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን እንዲፈታ ሕብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የመንገድ ማስፋፍያ ሥራዎችን መሰራታቸውን የጠቀሱት ዳኛቸው፤ ከእርሱም ጋር ተያይዞ የከተማዋ ትራንስፖርት ችግር እንዲቀርፉ የተተገበሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ይሁንና የመንግሥት ውጥን እንዲሳካና በየጊዜው እየተባባሰ የመጣውን ችግር ለመፍታት የሕብረተሰቡ ትራንስፖርት አጠቃቀም መሻሻል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። ይህም ችግሩን ለመፍታት አዳጋች እንዳደረገው እያደረገው እንዳለም አንስተዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም፤ ሕብረተሰቡ አውቶቢስ የመጠቀም ባሕሉን ማሳደግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
በተለይም የነዳጅና የውጭ ምንዛሪ ችግር ፈተና በሆነበት በዚሁ ጊዜ መንግሥት አስፈላጊውን አማራጭ ለመውሰድ እንደሚገደድ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ይህን ችግር ለመቅረፍ ለከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ አውቶቢሶች በተጨማሪ፤ የአዳዲስ አውቶቢሶች ግዥን ጨምሮ ብልሽት የገጠማቸውን አውቶብሶች ለመጠገን የሚያስችል ከፍተኛ በጀት መያዙን ነው የቢሮው ምክትል ኃላፊ የገለጹት፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ስምሪትና የመንገድ አጠቃቀምን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ በአጀንዳነት ይዞ እንደሚገኝም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ:www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በትግራይ ክልል 6.8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በተመደበዉ ኮታ አልገባም ተባለ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል መሰረታዊ ፍጆታ የሚሆን በፌደራል መንግሥት 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንደሚገባ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ግን እንዳልገባላቸው፤ የትግራይ ክልል የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ክንደያ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ለማህበረሰቡ ድጋፍ በሚል በፌደራል መንግሥት በተገባው ቃል መሰረት፤ የዘይት ድጎማ ወደ ክልሉ ይገባል ተብሎ የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን አለመግባቱንና ከታሰበው 6 ነጥብ 8ሚሊዮን ሊትር ዘይት መካከል እየተቆራረጠ ከአዲስ ዓመት በኋላ 2 መቶ 43 ሺሕ ሊትር ዘይት ብቻ እንደገባ ገልጸዋል፡፡
ለማህበረሰቡ የገባውን 2 መቶ 43 ሺሕ ሊትር ለማከፋፈል ወይንም ለማዳረስ እንደተቸገሩ አንስተው፤ ለምን መንግሥት ይገባል ባለው ኮታ መሰረት ወደ ክልሉ እንደማይገባ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምላሽ እየተሰጣቸው እንዳልሆነ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡
"የፌደራል መንግሥት በገባው ቃል መሰረት መሰረታዊ ፍጆታ ለማህበረሰቡ ድጋፍ ሲባል እንደማንኛውም ክልል በተመደበዉ ኮታ መሰረት ሊልክ ይገባል" ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአለምነው ሹሙ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ:www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ለመስቀል ደመራ በዓል ለተሽከርካሪ ዝግ የሚደረጉ መንገዶች ይፋ ተደረጉ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ነገ መስከረም 16/2017 ዓ/ም በመስቀል አደባባይ በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡
የ2017 ዓ/ም የመስቀል ደመራ በዓል በሠላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ መግባቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ/ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ መርሀ ግብሩ ፍፃሜ ድረስ ለተሽከርካሪዎች ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ፦
• ከቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ላይ
• ከቦሌ አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኦሎምፒያ አደባባይ ላይና ታች እንዲሁም ግራና ቀኝ መንገዶች
• ከመስቀል ፍላወር ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ ጋዜቦ አደባባይ ላይ
• ከአጎና ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ለከባድ ተሽከርካሪ አጎና ሲኒማ አጠገብ እንዲሁም ለቀላል ተሽከርካሪ ጥላሁን አደባባይ (አራተኛ ክፍለ ጦር ላይ)
• ከለገሀር መብራት ወደ መስቀል አደባባይ ለገሀር መብራት ላይ
• ከቴሌ ማቋረጫ ወደ ስታድዮም ለሚጓዙ ቴሌ ማቋረጫ
• ከራስ ሆቴል ወደ ስታድዮም ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ራስ ሆቴል ላይ
• ከሃራምቤ መብራት ወይም ከአምባሳደር ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ሃራምቤ መብራት ላይ
• ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ብሔራዊ ቤተ መንግስት አጠገብ
• ከዛንቺስ ሼል ወደ ባምቢስ የሚወስደው መንገድ ከዛንቺስ ሼል አጠገብ እንዲሁም
• ከጁፒተር ሆቴል ወደ ECA የሚወሰደው መንገድ ባምቢስ ሳልኮት ህንፃ አጠገብ ያሉ መንገዱች ለተሸከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም በተገለፁት መስመሮች ላይ ተሽከርካሪዎችን ለአጭርም ይሁን ለረዥም ጊዜ ማቆም የተከለከለ መሆኑን አሽከርካሪዎች ተገንዝበው አማራጭ መንገዶችን በመጠቀምና የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚያሳይዋቸው መንገድ በመጓዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን ያቀርባል።
በዓሉ ያለ አንዳች የፀጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወሰው ፖሊስ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በዓሉ ኃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር እና የበዓሉ ታዳሚዎች ሠላምና ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጿል።
ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-11-01-11 እንዲሁም በ991 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፋል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ሴኔጋል የባህር ዳርቻ ባንዲት ጀልባ ላይ 30 የቆዩ አስከሬኖች መገኘታቸው ተገለጸ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሴኔጋል የባህር ዳርቻ ላይ ለጊዜው ከየት ተነስታ እንደነበር ያልታወቀች ጀልባ ላይ 30 የቆዩ አስክሬኖች መገኘታቸውን የሴኔጋል የወታደራዊ ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
የሴኔጋል የባህር ሃይል በዋና ከተማው ዳካር 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ አንዲት የእንጨት ጀልባ እንደምትታይ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ወደ ቦታው አቅንቶ አስክሬኖቹን ማግኘት እንደቻለ አስታውቋል፡፡
አስክሬኖቹ ከመቆየታቸው የተነሳ ከየት እንደመጡ ለመለየት ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ሂደት እንደሆነ የባህር ሃይሉ መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሴኔጋል ተነስተው ወደ ስፔን የካናሪ ደሴቶች ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ስደተኞቹ ወደ ስፔን ለመግባት ከ1500 ኪሎሜትር በላይ በአትላንቲክ ውቂያኖስ ላይ ይጓዛሉ ተብሏል፡፡
አሁን በእንጨት ጀልባዋ ላይ የተገኙት 30 አስክሬኖች ሁኔታ ለብዙ ቀናት በአትላንቲክ ውቂያኖስ ላይ ተንሳፈው መቆየታቸውን እንደሚያሳይ ተገልጿል፡፡
ጀልባዋ መቼና ከየት እንደተነሳች እንዲሁም ምን ህል ሰዎች እንደነበሩባት ለማወቅ ምርመራዎች እየተደረጉ እንደሚገኙ የሴኔጋል ባህር ሃይል ተናግሯል፡፡
በገነነ ብርሃኑ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የትራንስፖርት አገልግሎት ሰዓትን በሚሸራርፉ የታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰዓትን በሚሸራርፉ የታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት መጠናቀቁ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
ይህ የሆነዉ የተማሪዎች መውጫና መግቢያ ሰዓትን ተገን በማድረግ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያስተጓጉሉና ታሪፍ የሚጨምሩ የታክሲ አሽከርካሪዎች መኖራቸው መረጋገጡን ተከትሎ ነው።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ከታክሲ ማሕበራት ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩን ይፈታል ተብሎ ቢጠበቅም፤ ባለፈው ዓመት የነበረውን ችግር እየተደገመ መምጣቱን ተከትሎ ችግሩን ለመፍታት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መወሰኑን የቢሮው ምክትል ሃላፊ ዳኛቸው ሽዋፈራሁ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ምክትል ሃላፊ አክለውም፣ የተማሪዎች መውጫና ወደ ቤታቸው መመለሻ ሰዓት ላይ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት መስተጓጎል ችግር ለመፍታት አማራጭ ሐሳቦችን እየተፈለገ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተደረገው ግምገማ የከፋ ችግር አለመኖሩ መረጋገጡንም አቶ ዳኛቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ግንባር ቀደም ከሚባሉ ችግሮች ቀዳሚዉ የትራንስፖርቱ ዘርፉ መሆኑ ይጠቀሳል።
በዚህም መሠረት የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን መፍትሔ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል።
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ:www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በሴኔጋል ብሔራዊ ምርጫ በርከት ያሉ ፓለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት እየፈጠሩ መሆኑን ተሰማ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጥቂት ቀናት በቀረው የሴኔጋል ብሔራዊ ምርጫ፤ ከወትሮው በተለየ መልኩ ይጣመራሉ ተብለው ያልተገመቱት ፓርቲዎች ጥምረት እየፈጠሩ መሆኑን ተገልጿል።
ይሕም በአገሪቱ አዲስ የፓለቲካ ምሕዳር ሊፈጥር ይችላል እየተባለ ይገኛል።
በሴኔጋል ምርጫ ውድድር ከወዲሁ ቀልብ ሳበ ጉዳይ ሆኗል።
በአገሪቱ ፓርቲዎቹ ሊበራሊቶችና ዴሞክራቶች በሚል መቧደናቸው በፓለቲካው አዲስ ቅርፅ እየተፈጠረ መምጣቱን ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
የሴኔጋል ብሔራዊ ምርጫ ሊካሄድ ከአራት ቀናት ያነሱ ቀናት ብቻ እንደቀሩትና የምርጫ ፍክክሩ ድባብ ከወዲሁ ቀልብ መሳቡን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በጋምቤላ አንድ አምቡላንስ የባሮ ወንዝ ጊዜያዊ ድልድይን ጥሶ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጋምቤላ ክልል በጂካዎ ወረዳ ትናንት ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ አንድ አምቡላንስ ተሽከርካሪ የባሮ ወንዝ ጊዜያዊ ድልድይን ጥሶ በወንዝ ውስጥ በመግባቱ፤ የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኡጉላ ኡጁሉ እንደገለጹት፤ "አደጋው የደረሰው ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን በመጓዝ ላይ የነበረ አምቡላንስ፤ በጂካዎ ወረዳ የባሮ ወንዝ ጊዜያዊ ድልድይን ጥሶ በወንዝ ውስጥ በመግባቱ ነው" ብለዋል።
በአደጋውም የ7 ሰዎች ሕይወት ወዲያው ማለፉን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ከሟቾቹ መካከል የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
የሟቾቹ አስክሬን ለማውጣት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአደጋው ሌሎች 7 ሰዎች ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና በመከታተል ላይ መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኮሚሽነር ኡጉላ፤ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሊያሽከረክሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የንግዱ ማኅበረሰብ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ አይደለም ተባለ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስገድድ አዋጅ ቢኖርም እየተከበረ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት አስታውቋል፡፡
ጠንካራ የሲቪል ማኅበረስብ ድርጅቶች እንዲኖር መንግሥት ሚናውን መወጣት እንዳለበት ያስታወሱት፤ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ ናቸው፡፡
ምክትል ዳይሬክተሩ፤ "ማንኛውም የንግድ ማኅበረሰብ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚደግፍ ከሆነ በዓመት ከሚከፍለው ግብር ላይ 15 በመቶ እንደሚቀነስለት" ሕጉ ቢፈቅድም፤ ተግባራዊ አለመደረጉ ዘርፉን እየጎዳው እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
የአሰራሩ ተግባራዊ መደረግ የንግዱ ማኅበረሰብ ሴክተሩን የሚያግዝበትን ተነሳሽት የሚጨምርለትና ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያበረታታ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
"ነገር ግን አሁን ላይ በርካታ ባለሀብቶች ኃላፊነታቸውን አልተወጡም" የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ "በተለይም በሰብዓዊ መብት እና ከዲሞክራሲያዊ መብት ጋር የተያያዘ ሥራ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር መስራት የሚፈልግ ነጋዴ የለም፡፡ «ከመንግሥት ጋር ያነካካኛል» የሚል ስጋት አለ" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማኅበራቱ ችግሩን ለመቅረፍ ባለሀብቶች ሕጉን እንዲያውቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብሮች ሊዘረጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ባልስልጣን ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ እየተጠበቀ እንዲገኝም ነግረውናል፡፡
መንግሥት መንግሥታዊ ኃላፊነቱን፣ የንግዱ ማኅበረሰብም ማኅበረሰባዊ ኃላፊነቱን ተወጥቶ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን የድርሻውን እንዲወጣም ምክትል ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የትግራይ ተማሪዎች በዳስ ውስጥ እየተማሩ እንደሚገኝ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ
መስከረም 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ በተጠናቀቀውና “የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት” ተብሎ በሚጠራው ደም አፋሳሽ ግጭት ምክንያት ከ2 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል በመውደማቸው፤ በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በዳስ ውስጥ ለማስተማር መገደዱን የትግራይ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ጉዕሽ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ በጦርነቱ ምክንያት የአብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎች በርና መስኮት የሌላቸው፣ ከፊል እና በሙሉ ጣሪያቸው የተበላሸ ናቸው፡፡
ከፊሎቹ የመማሪያ ክፍሎች ግድግዳዎችም የተበሳሱ፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት በሚረብሽ ሁኔታ ጸሐይና ንፋስ የሚፈራረቅባቸው ስለመሆናቸው ነግረውናል፡፡
በተያያዘ በጦርነት ምክንያት በተማሪዎች ላይ የተዛባው የጊዜ ጉዳይ አሁንም ማስተካከል አለመቻሉን የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በተለይ በክልሉ የነበሩ ተማሪዎች በጦርነቱ እና በኮቪድ ወረርሺኝ ምክንያት ለአራት ዓመታት ትምህርት መቋረጡ አስታውሰው፤ ከጦርነት በኃላ ትምህርት ቢጀመርም መማር ከነበረባቸው እድሜ አራት ዓመት የዘገየ ትምህርት በመማር ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በክልሉ ያሉ ተማሪዎች መድረስ ያለባቸው የትምህርት ዘመን ላይ መድረስ አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን፤ የመማሪያ ክፍል እጦትና በቂ የትምህርት ቁሳቁስ ማጣታቸው የተሻለ ትምህርት ማግኘት እንዳይችሉ እንዳደረገም ኃላፊው ተናግረዋል።
በሚኪያስ ኃይሌ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የአይምሮዊ ንብረት አሰራር የሚመራበት ስርዓት ድጋፍ እና መሻሻል ያስፈልገዋል ተባለ
መስከረም 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን እና የቻይና ብሄራዊ አእምሯዊ ንብረት አስተዳደር የሁለትዮሽ ትብብር የተግባር ዕቅድ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ በቀጣይ ሁለት ዓመታት በተለያዩ አእምሯዊ ንብረት መስኮች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ሲሆን፤ የስምምነት ፊርማው በባስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል እና በአስተዳደሩ ኮሚሽነር ሼን ቻንግዩ በቤጂንግ መሃከል ተከናውኗል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም አሐዱ ስምምነቱ አላማ ምንድነው ለዉጡ እና ተግባራዊነቱስ እስከምን ድረስ ነዉ ሲል ጠይቋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአሰራር፣ ከዐቅም ዉስንነት እና ተያያዥ ነገሮች እንዲሁም ከህግ አንጻር ትልቅ ችግር እንደሚስተዋልበት የገለጹት፤ የኢትዮጵያ አእምሮዋዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢልያስ መሀመድ ናቸው፡፡
ይህም የአይምሮዊ ንብረት አሰራርና የሚመራበት ስርዓት ድጋፍ እና መሻሻል እንደሚያስፈልገው የገለጹት ኃላፊው፤ አሁን ከቻይና ጋር የተፈረመው ስምምነት እነዚህን ችግሮች ከመቀነስ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ከማጠናከር አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ለአሐዱ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሁለቱ ተቋማት የሁለትዮሽ ትብብር የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ፕሮግራሞችን ለማበራከት፣ በአእምሯዊ ንብረት ስርዓት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽግግር ለማሳለጥ እንዲሁም የማህበረሰብ ዕውቀት ጥበቃን ለመደገፍ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድን አባል ሀገራትን በተቀላቀለችበት ማግስት የተከናወነ ስምምነት በመሆኑም፤ የተቋማቱን ትብብር ከፍ እንዲል እንደሚያደርገውና የሀገራችንን የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ስርዓት ለማሰደግና ለማጠናከር ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ እንዲሚኖረው ተመላክቷል፡፡
በፅዮን ይልማ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ከ40 በላይ የማከፋፈያ ተሽከርካሪዎች ማዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ
መስከረም 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለመስቀል በዓል የሚከናወኑ እርዶችን በከተማዋ ለሚገኙ ልኳንዳ ቤቶች ለማዳረስ ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
አዳዲስ ጊዜያዊ ሠራተኞችን መቅጠር፣ አሰራሩን ፈጣን እና ዘመናዊ ማድረግ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል እንደሚገኙበት ሰምተናል፡፡
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ህዝብ ግኑኙነት ኃላፊ አታክልቲ ገብረሚካኤል ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ የእርድ እንስሳትን ስጋ ወደ ልኳንዳ ቤቶች ለማዳረስ ከ40 በላይ ተሽከርካሪዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
አያይዘውም ለበዓሉ የመጣውን የትኛውንም ያክል ቁጥር ያለው እንስሳ አርዶ ለማስረከብ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ያሉ ሲሆን፤ "ማኅበረሰቡም የሚሸምተውን ስጋ በሕጋዊ መንገድ የታረደ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ይኖርበታል" ሲሉ መክረዋል፡፡
በሚኪያስ ኃይሌ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ያለምንም ካሳ ቤታቸዉ የፈረሰባቸው የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አሰሙ
መስከረም 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሸገር ከተማ ወይብላ ማርያም አካባቢ በኮሪደር ልማት ምክንያት ከዕለተ ቅዳሜ ጀምሮ ፈረሳ እየተከናወነ እንደሆነ እንዲሁም፤ ለአካባቢው ነዋሪ ምንም አይነት ካሳም እንዳልተከፈለ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአሐዱ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከፈረሳው በፊት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ውይይት እንዳደረጉ የገለጹ ሲሆን፤ በውይይቱ ወቅትም የከተማ አስተዳደሩ እና የወረዳው ኃላፊዎች በተገኙበት "ካሳ ተከፍሎ ከአካባቢ እንደሚነሱ" እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
ነገር ግን በቀጣዩ ቀን ጠዋት ያለምንም ዝግጅት የከተማ አስተዳደሩ ሰዎች ግሬደር አምጥተው ቤታቸው እንዳፈረሱባቸዉ ተናግረዋል።
በዚህ ፈረሳ ወቅትም አራት ሰዎች የአካል ጉዳት እንዳጋጠማቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ጨምረው ለአሐዱ ገልጸዋል።
ቤቶቹን የፈረሱባቸው ሰዎች ሕጋዊ ካርታ ያላቸው እንዲሁም የቀድሞ ይዞታ ባለቤቶች እንደሆኑም ተናግረዋል። እነዚህንም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች እና አስፈላጊ መረጃዎች ለአሐዱ በዝርዝር አሳይተዋል፡፡
አሐዱም በቅሬታው መሰረት በማድረግ የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛን አናግሯል።
ከንቲባው ቤቶቹ መፍረሳቸውን አምነው "የፈረሱ ቤቶች ህጋዊ መሆናቸውን አረጋግጠን ካሳ እንከፍላለን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
"በአካባቢው ላይ አብዛኛዎቹ ቤቶች ሕጋዊ አይደሉም" ያሉት ከንቲባው ከነዋሪዎቹ ቅሬታ እንዳልደረሳቸውም ተናግረዋል።
አሐዱ የጉዳዩን ተፈፃሚነትበቀጣይ እየተከታተለ ወደእናንተ የሚያደርስ ይሆናል።
በሚኪያስ ኃይሌ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከተመድ እውቅናና ሽልማት አገኘ
መስከረም 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል እና በመቆጣጠር ላስመዘገበችው አመርቂ ውጤት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እውቅና አግኝታለች።
በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 79ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፤ የድርጅቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ግብረ ሃይል (ኤንሲዲ) ለኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ሽልማት አበርክቷል።
እውቅናው ኢትዮጵያ የተቀናጀ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎችን በማከናወን እና ማህበረሰቡን ያማከለ አገልግሎት መስጠት በመቻሏ በተለይም የማህፀን ጫፍ ካንሰርን በመከላከል ላስመዘገበችው ውጤት መሆኑ ተገልጿል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 79ኛው ጠቅላላ ጉባኤ (UNGA77) ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የጤና ሚንስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ሽልማቱን መቀበላቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ለተሽከርካሪ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎት በጥሬ ገንዘብ መክፈል ክልከላ መደረጉ ተገለጸ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎት በጥሬ ገንዘብ መክፈል ክልከላ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ አዋጅ ወጥቶ መጽደቁ አይዘነጋም።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከዚህ ቀደም ለመኪና ማቆሚያ አገልግሎት እንዲሆኑ በተዘጋጁ በተለዩ ስፍራዎች የተለያዩ መጭበርበሮችና አላስፈላጊ ወጪዎችን መስተዋላቸውን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የመንገድ ዘርፍ ደህንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ዘርጋ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለዩ ህንፃዎች ላይ የተሸከርካሪ ማቆያ የፓርኪንግ አገልግሎት ክፍያን በቴክኖሎጂ ለመቀየር የሚያስችል ስርዓት በዚህ ዓመት ተግባራዊ እንደሚደረግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለዉም፤ ከዚህ ቀደም የዘፈቀደ እና ተመን የሌለው ክፍያ ግለሰቦች እንደሚጠየቁ ገልጸው፤ ይህ የአሰራር ስርዓት ወደ ትግበራ ሲገባ ወጥ የሆነ የክፍያ አሰራር እንደሚኖር ጠቁመዋል።
በፅዮን ይልማ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በሁለት ዓመት ውስጥ ከ50 ሺሕ በላይ ዜጎች መሸኛቸዉን ይዘው መታወቂያ እየጠበቁ መሆኑ ተገለጸ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2014 ዓ.ም ጀምሮ የታገደው ከክፍለ ሀገር መሸኛ ይዘው ለሚመጡ ዜጎች መታወቂያ መስጠት ሂደት አሁንም ድረስ ወደ ሥራ አለመግባቱ ቅሬታ አስነስቷል፡፡
በሁለት ዓመት ውስጥም ከ50 ሺሕ በላይ ዜጎች መሸኛ አምጥተው መታወቂያ እየጠበቁ ቢሆንም፤ እገዳው አሁንም አለመነሳቱ ታዉቋል፡፡
እገዳው ችግሮችን ለመቀነስ በማሰብ የተደረገ መሆኑ የተነሳ ሲሆን፤ በዚህ ምክንያት በከተማዋ በርካታ ወንጀሎች እንደነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ለአሐዱ ገልጿል፡፡
በመሆኑም እንደ ሀገር ወጥ የሆነ አስራር ባለመዘርጋቱ የተነሳ፤ ሥራውን ለማስጀመር እንቅፋት እንደሆነበት ኤጀንሲው ጨምሮ አስታውቋል፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ እነዚህን ችግሮች ቀርፎ መሸኛ ለሚያመጡ ዜጎች መታወቂያ መስጠት ለምን አልተቻልም? ሲል አሐዱ የኤጀንሲው የነዋሪነት አገልግሎት ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሴን ጠይቋል፡፡
ዳይሬክተሩ እገዳዉ በቅርብ ግዜ ውስጥ እንደሚነሳ ቢጠበቅም፤ በተቋሙ አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም ብለዋል፡፡
"ኤጀንሲው ብቻውን በዚህ ወቅት ይጀመር አይጀመር የማለት አቅም የለውም" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ "ይህ ጉዳይ የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ተቋማት ጉዳይ በመሆኑ በጋራ የሚወሰን ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ይህንን ችግር መፍታት የሚቻልበት ጥናት እንደ ከተማ አስተዳደር እየተካሄደ መሆኑንና ጥናቱ ግን ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሠረትም ከ50 ሺሕ በላይ መልቀቂያ የጠየቁ ዜጎቸ ፋይል ወደ ከተማው ገብቶ መቀመጡን የገለጹም ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ወደ 37 ሺሕ የሚሆኑት ከጀርባ ተፍሮሞ ሥም ዝርዝራቸው ኤጀንሲው ጋር መድረሱን ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የማጥራት ሥራዎች በስፋት አለመሰራታቸውን ያነሱት አቶ ዮሴፍ፤ "ሕጋዊ መሸኛ እና ሕጋዊ ያልሆነ ፎርጅድ መሸኛ ይዘው የሚመጡትን መለየት አልተቻለም ነበር" ብለዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም የታገደው በጊዜው ማንዋል መታወቂያ ብቻ ይሰጥ የነበረ በመሆኑና በወቅቱ የሚመጡት በርካታ መሸኛዎች ፎርጅድ በመሆናቸው መሆኑን አቶ ዮሴፍ ንጉሴ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በደረሰ አደጋ የ28 ሰዎች ሕይወት አለፈ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከወላይታ ሶዶ ከተማ ወደ ዳውሮ ዞን ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በደረሰ አደጋ የ28 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ፡፡
አደጋው ዛሬ ቀን 7 ሠዓት ላይ በወላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ፣ ፈታታ ቀበሌ በሚገኝ ግእርባ ወንዝ ውስጥ፤ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሱ ተንሸራቶ በመግባቱ የተከሰተ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከሟቾች በተጨማሪ በ29 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ የተከሰተው አደጋ ከባድ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተመላክቷል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ:www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
አሜሪካ ከሩሲያ እና ከቻይና የሚገቡና ለመኪና መሥሪያ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎችን ልታግድ ነው
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አሜሪካ ከሩሲያ እና ከቻይና የሚገቡና ለመኪና መሥሪያ የሚውሉ የሶፍትዌር እንዲሁም የሃርድዌር ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገሯ እንዳይገቡ በሕግ ልታግድ መሆኑ ተሰምቷል።
አሜሪካ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ከሁለቱ አገራት የሚመጡ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች “ለብሔራዊ ደኅንነቴ” ያሰጉኛል በማለቷ ነው።
ባለሥልጣናት እንደሚሉት ቴክኖሎጂዎቹን መከልከል ያስፈለገው፤ በተለይም አሽከርካሪ አልባ ዘመናዊ መኪኖችን ለማምረት የሚገቡ መሣሪያዎች ምናልባት ከሁለቱ አገራት በርቀት ቁጥጥር ሊደረግባቸው እና ላልተፈለገ ዓላማ ሊውሉ ይችላሉ የሚል ስጋት በመኖሩ መሆኑን ኤፒ ኒዉስ ዘግቧል።
ገደብ የሚጣልባቸው ቴክኖሎጂዎች ‘ሾፌር አልባ መኪኖችን’ ለማምረት የሚያገለግሉ እና ተሽከርካሪዎች እርስ በእርስ እንዲግባቡ የሚያደርጉ፤ የመኪና የትስስር መረብን (ኔትዎርክ) ለመፍጠር የሚያስችሉ ሶፍትዌሮች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
በዳግም ተገኝ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የኔዘርላንድ ፍርድ ቤት በኤርትራውያን መካከል በተፈጠረው ግጭት ተሳታፊዎች ላይ የእስር ቅጣት ወሰነ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኔዘርላንድ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር በኤርትራውያን መካከል በተፈጠረው ግጭት ተሳታፊዎች ላይ የእስር ቅጣት ወስኗል።
በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች ዘ ሄግ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ ተቃዋሚ ኤርትራውያን ተገኝተው በተሽከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶች እንዲሁም በፖሊስ ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ፤ የግጭቱ አስተባባሪ እና ዋነኛ ተሳታፊዎች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ተይዘው ክስ እንደተመሰረተባቸዉ ተገልጿል።
እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር መስከረም 13 ብይን የሰጠው የአገሪቱ ፍርድ ቤት፤ ዋነኛ የግጭቱ መሪ ነው በተባለው የ48 ዓመቱ ዮሐንስ አብረሃ ላይ የአራት ዓመታት እስር ሲፈርድ በሌሎች ላይ በተለያየ መጠን የወራት የእስር ቅጣት አስተላልፏል።
ፍርድ ቤቱ እንዲታሰሩ የወሰነባቸው ኤርትራውያኑ ስደተኞች "በግጭቱ እና ግጭቱን ተከትሎ በንብረት ላይ ለተከሰተው ጉዳት ተጠያቂ ናቸው" የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፤ ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ክሱን እንደማይቀበሉት አሳውቀው እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።
በዳግም ተገኝ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በህወሓት አመራሮች መሀል ያለው መከፋፈል በክልሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እክል ሆኗል ተባለ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል በተቀሰስቀሰው ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ የተለያዩ ሥራዎች ቢጀመሩም አሁን በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው መከፋፈል ነገሮች በተፈለገው ልክ እንዳይሄዱ አድርጓል ተባለ።
ከአሐዱ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሳልሳይ ወያነ ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃን አጽብሃ፤ በደቡብ ትግራይና ጠለምት የሚገኙ ተፈናቃዮች የሚፈለገው መሰረታዊ ድጋፍ እና የደህንነት ጥያቄያቸው ምላሽ አለማግኘቱ እንደ አብነት አንስተዋል።
ለዚህም በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት በክልሉ የሚስተዋለው ችግር ወደ ጎን እንዲተው አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል።
ስለሆነም በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ዳግም ሰላም ወደ ማጣት እንዳይሄድ ሁሉንም አካታችና አሳታፊ የሆነ መንግሥት መመስረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
እንዲሁም የትግራይ ህዝብ በህወሓት እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ወገን ባለመያዝ ሰላሙን ጠብቆ መቆየት አለበት ብለዋል።
አክለውም በፕሪቶሪያው ስምምነት ወቅት አደራዳሪ የነበሩ አካላት አሁንም በስምምነቱ የተካተቱ ጉዳዮችን ተግባራዊ እንዲደረጉ ግፊት ሊያደርጉ እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል።
ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ አባላቱ ጉባኤ ማካሄድ አለብን ወይስ የለብንም የሚለው ፖለቲካዊ ክርክራቸው ከፍ ቢልም ጉባኤው መካሄዱ ይታወሳል።
በዚሁ ጉባኤ ላይም ህወሓት ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የሚሆኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ ካድሬዎችን ከአመራርነት አንስቷል።
በተጨማሪም ዶክተር ደብረፂዮንን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ በድጋሚ የሾመ ሲሆን፤ አዳዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴና የቁጥጥር ኮሚሽኖች አባላትም መርጧል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን የህወሓት ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን ውሳኔን ወደ ጎን ብሎ የተካሄደውና "ሕጋዊነቱ" ላይ ጥያቄ የተነሳበት ይህ ጉባኤ ከፍተኛ አለምግባባትን አስከትሏል።
በዚህም ህወሓት በአመራር አባላቶቹ እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ክልሉን ለዳግም ጦርነት እንዳይዳርግ ምሁራን ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሕወሓትም ሆነ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እርስ በእርስ መወቃቀሳቸውን ቀጥለውበታል፡፡
በፍርቱና ወልደአብ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የካሳንቺስ አካባቢ 239 የልማት ተነሺዎች "ለሁሉም አባወራዎች ስቱዱዮ ቤት ነው የተሰጠው" ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የካሳንቺስ አካባቢ 239 የልማት ተነሺዎች "ከባለ አንድ እስከ ባለ ሦስት መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ብንጠይቅም፤ ለሁሉም አባወራዎች ስቱዱዮ ቤት ነው የተሰጠው" ሲሉ ቅሬታቸውን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ወራት በኮሪደር ልማት ምክንያት በርካታ የአዲስ አበባ አካባቢዎች እየፈረሱና እንደ አዲስ እየተገነቡ መሆኑ ይታወቃል።
የዚህ ሥራ ምዕራፍ 1 ተጠናቆ የምዕራፍ ሁለት ሥራ መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን፤ በምዕራፍ ሁለት የልማት ሥራ ከሚከናወንባቸው የከተማው አካባቢዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ ካሳንቺስ መሆኑ ተገልጿል።
ከሰሞኑም ከካሳንቺስ አካባቢ የተነሱ ዜጎች ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ውይይት ማድረጋቸውና ተደጋጋሚ ውይይቶች እንደሚደረጉ ተነግሯቸው የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ በቀጣዩ ቀን ጠዋት ቤታቸው እንደፈረሰባቸው ቅሬታ በማቅረባቸው፣ አሐዱ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ዘገባዎችን መስራቱ ይታወሳል።
አሁን ላይ ነዋሪዎቹ ባቀረቡት ቅሬታ ደግሞ፤ የቤተሰብ ብዛታቸውን ያላገናዘበ መኖሪያ ቤት እንደተሰጣቸው የገለጹ ሲሆን፤ ለሁሉም የልማት ተነሺዎች በተለይ ለ239 ነዋሪዎች ስቱዲዩ ቤት እንደደረሳቸው ለአሐዱ ገልጸዋል።
በተጨማሪም አቅመ ደካሞች ሆነው ሳለ፤ የጠየቁት ቤት እና የተሰጣቸው የተለያየ እንደሆነ ገልጸው፤ የፎቁ ከፍታ በጭራሽ ሊወጡት የማይችሉት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ስቱዲዮ ቤቶቹ በቂ መሰረተ ልማት ያልተዘረጋባቸው ሆነው እንዳገኟቸውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጨምረው ለአሐዱ አስረድተዋል።
አሐዱ ቅሬታውን መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን አነጋግሯል።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የከተማው አስተዳደሩ ኃላፊ፤ የልማት ተነሺዎቹ የወጣውን ዕጣ ከተመለከቱ በኃላ፤ ቅሬታ ፎርም ሞልተው መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም፤ "የተሰጣቸው ስቲዲዩም ቢሆን አሁን ከሚኖሩበት ቤት ይሻላል" ያሉ ሲሆን፤ "አንዳንድ ዜጎች ከሚኖሩበት እና ከቤተሰባቸው ጋር የማይመጣጠን ጥያቄዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ቢሮ የቤት ማስተላለፍና ብድር አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ቶማስ ደበሌ በበኩላቸዉ፤ "ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቀድሞውኑ በጋራ ባደረጉት ውይይት ስቱዲዮ ቤት እንደሚፈልጉ ተስማምተው ነው ለዕጣ ማውጣቱ የመጡት" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም፤ "ችግሮች የነበሩበት የሰነድ ማስተላለፍ ላይ የነበረ ሂደት ዛሬ ላይ ቅሬታ ፈጥሯል ዜጎች ሞልተውት የነበረውን የቤት አይነት ሰጥተናል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አሐዱ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥበት ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ቢያደርግም፤ የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚ በስልጠና ምክንያት ከከተማ ውጭ በመሆናቸዉ ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡ ነገር ግን በቀጣይ ጉዳዩን ተከታትለን ወደእናንተ የምናደርስ ይሆናል፡፡
በሚኪያስ ኃይሌ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በጋና መንግሥትን ያወገዙ ተቃዋሚዎች መታሰራቸው ተሰማ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጋና የመልካም አስተዳደር ችግር እየበረታ መምጣቱን ተከትሎ በመንግሥትን ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎች መታሰራቸው ተሰምቷል።
የመንሥትን የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት አያያዝን በፅኑ በማውገዛቸው የተነሳም ዘብጥያ እንዲወርዱ መደረጋቸው ነው የተነገረው።
ተቃዋሚዎቹ በተለይም የጋና ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ኧርነስት አዲሰና ከሁለቱ ምክትሎቻቸው ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ መጠየቃቸው ተነግሯል።
የጋና ጸጥታ ኃይሎች በበኩላቸው፤ ለእስር የተዳረጉት በሰልፉ ላይ ብጥብጥ ለመፍጠር የሞከሩና በሁከት የተጠረጠሩ ናቸው ሲል መግለጹን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
የጋና ምጣኔ ሐብት የሸቀጦች ዋጋ መናሩን ተከትሎ የዋጋ ግሽበት ወደ 54 በመቶ ከፍ ማለቱም በዘገባው ተጠቅሷል።
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በኢትዮጵያ በዓመት እስከ 3 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች በዉሻ እብደት በሽታ እንደሚሞቱ ተገለጸ
መስከረም 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ክትትሎች በዓመት 3 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች በተለምዶው የእብድ ውሻ በሽታ ተብሎ በሚጠራው (የዉሻ እብደት በሽታ) እንደሚሞቱ የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።
"የዉሻ እብደት በሽታ ገዳይ ቢሆንም ያን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም" የሚሉት በግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ የዉሻ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ ዶ/ር ወንዱ መንገሻ ናቸው።
ይህ ቁጥር ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ ወደ ሆስፒታል ሄደው መሞታቸው የተመዘገቡት ብቻ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ወንዱ፤ ወደ ጤና ተቋማት ያልደረሱ ሰዎችን ያላካተተ መሆኑን አንስተዋል።
አክለውም፤ በሽታው በብዛት ከሚከሰትባቸውና የበሽታው ስርጭት ያለባቸው ሀገራት ዉስጥ፤ ኢትዮጵያ መመደቧን አስረድተዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያም የአንድ ጤና ዘዴ በመጠቀም በ2030 የውሻ በሽታን ለማስወገድና ለመቆጣጠር የተለያዩ ስልቶችን ቀይሳ እየሰራች እንደምትገኝ ለአሐዱ ገልጸዋል።
በሽታውን ቀድሞ ለመከላከልም ማህበረሰቡ የውሾችን የመኖሪያ ንጽህና መጠበቅ እና በየዓመቱ ውሾችን ማስከተብ እንደሚጠበቅበት ዶ/ር ወንዱ አሳስበዋል።
ይህ የውሻ በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በተደረገው ጥናት መሠረት ከ99 ነጥብ 9 በመቶ በላይ በውሻ ንክሻ ይተላለፋል። እንዲሁም በውሻ የመቧጨር አደጋ ሲያጋጥም እና በለሀጭ አማካኝነት ሊተላለፍ እንደሚችል ተመላክቷል።
የውሻ እብደት በሽታ በማደግ ላይ ባሉ እንደ አፍሪካና ኤዥያ እንዲሁም ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላይ በሚገኙ ሀገራት ላይ በስፋት ይስተዋላል።
በፍርቱና ወልደአብ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
85 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ በአሽከርካሪዎች ጥፋት እንደሚደርስ ተነገረ
መስከረም 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያጋጥሙ የትራፊክ አደጋዎች መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት በአሽከርካሪዎች ጥፋት እንደሚደርሱ የትራንስፖርት ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት ሚንስትር ዴኤታ አቶ በርሆ ሐሰን ለአሐዱ እንደተናሩት አደጋውን ለመቀነስና ለመከላከል ሕጎችን ከማሻሻሻል ጀምሮ በርካታ ለውጥ አምጪ እንቅስቃሴዎች በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአካል፣ በህይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ፤ በሀገር ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖውን እያሳረፈ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የመንገዶችን ደህንነት እና ጥራት የማስጠበቅ ሂደትን በተመለከተም መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት እንደሚገኝም ሚንስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሁሉም የመንገድ ተጠቃሚዎች የየራሳቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በታሪኩ አለሙ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን ከጥቃት ኢላማዎች እንዲያርቁ መልዕክት ተላለፈ
መስከረም 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሊባኖስ እና በቀጠናው ያለው ወቅታዊ የጸጥታ ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመምጣቱ በሊባኖስ፤ የቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል።
ጽ/ቤቱ በተለይም በደቡባዊ ሊባኖስ እንዲሁም በቤይሩት አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተጠናከረው መቀጠላቸውን ገልጿል፡፡
ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤቱ የሁኔታውን አሳሳቢነት በመረዳት፤ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝም አስታውቋል።
ሆኖም በቀጠናው እና በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጲያዊያን የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወስዱ ሲል አሳስቧል።
በዚህም መሰረት ዜጎች፡-
1. በአብዛኛው የጥቃት ዒላማ ሊሆኑ ይቻላሉ ተብለው ከሚታሰቡ ቦታዎች እራስን ማራቅ፣
2. ከሊባኖስ መንግሥት የሚሰጡ መመሪያዎችን እና አቅጣጫዎችን መተግበር ወይም ማከበር፣
3. አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የበለጠ እየከፋ የሚሄድ ከሆነ በቀጣይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ይፋ እስከሚደረጉ ድረስ ከቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤቱ የፌስ-ቡክ ፔጅ የሚለቀቁ መረጃዎችን በየጊዜው መከታተል፣
4. ማንኛውንም የከፋ ሁኔታ በሚገጥም ወቅት በቆንስላው ቀጥታ የስልክ መስመር +9615467166 እና በWhatsapp ቁጥር ማሳወቅ ጠቃሚ ይሆናል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: //www.facebook.com/ahaduradio
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ