መገናኛ ብዙሃን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎችን ሊሰሩ ይገባል ተባለ
ሕዳር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃኖች በማህበረሰቡ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገት ላይ ትኩረት ሰጥተዉ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመገናኛ ብዙሃን በምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ያላቸውን ሚና በሚመለከት ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነዉ ይህ የተገለጸው።
በዉይይቱ በተለይም አሁን የሚስተዋለዉን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም መገናኛ ብዙሃን፣ ሸማቾች እንዲሁም መንግሥት በኢኮኖሚዉ ረገድ ያላቸዉ ሚና ምን መምሰል አለበት የሚሉ ሀሳቦች ተነስቷል።
በምክክር መድረኩ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ሙያተኞች የሚሰሯቸዉ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ይዘት ያላቸው መረጃዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሀገር ምጣኔ ሀብት ጋር ግንኙነት እንዳላቸዉ ተገልጿል።
በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ ስለኢኮኖሚ እና ነባራዊ የገበያ ሁኔታዎች በቂ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።
በተጨማሪም ሰላም ለልማት ባለው ሚና፣ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እና የዓለም አቀፉ ንግድ ድርጅት መርሆዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ሚና በግሉ ዘርፍ እድገት በምክር ቤቱ እየተተገበሩ ስላሉ ሥራዎች ማብራሪያ ተሠጥቷል።
በፅዮን ይልማ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህመምተኞች ቁጥር መጨመሩ ተነገረ
ሕዳር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ ሐገራት ብቻ ከ537 ሚሊዮን በላይ የስኳር ታማሚዎች እንደሚገኙ የኢትዮጵያ የስኳር ህሙማን ማኅበር አስታውቋል፡፡
ማኅበሩ ይህን ያለው በሕዳር ወር የሚታሰበውን የስኳር ህመም ቀን አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ ለሚድያ ባለሙያዎች በተዘጋጀው ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህመምተኞች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።
አክለውም፤ "ቆሽት የተባለችው የሰውነት ክፍል ሥራዋን በትክክል ባለመስራቷ ምክንያት የሚከሰተው በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መዛባት በዓይን፣ በኩላሊት እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት ያስከትላል" ብለዋል፡፡
የስኳር ህመም አመጋገብን እና የኑሮ ዘይቤን በማስተካከል መከላከል እና መቆጣጠር እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡
ስኳር የተገኘባቸው ሰዎች ከአመጋገብ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በተጨማሪ አልኮል እና ሲጋራን ሙሉ ለሙሉ እንዲያቆሙ ይመከራል የተባለ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ሰው በየጊዜው በመመርመር ያለበትን ሁኔታ ማወቅ እንደሚገባው የሕክምና ባለሙያዎች መክረዋል፡፡
በአለምነው ሹሙ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
#አሐዱ_መድረክ
"በአማራ ክልል ግጭት ሳይሆን ጦርነት ነው እየተካሄደ ያለው" (ክፍል 2)
ሙሉ ቆይታውን ለመከታተል ከሥር ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ!
👇
https://youtu.be/OACq3rvp0Ik?si=liVFbo4f9avBaXYG
የጥብቅና ሙያ እንደማንኛውም የንግድ ሥራ መታየት የለበትም ሲል የፌደራል ጠበቆች ማህበር ተናገረ
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የፌደራል ጠበቆች ማህበር የጠበቃነት ሙያ ከፍትሕ ስርአቱ ጋር የሚገናኝ ጉዳይ በመሆኑ፤ ሙያው እንደ ሌላው የንግድ አይነት መታየት እንደሌለበት ለአሐዱ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ መሰረትም ሙያው እንደሌላው የንግድ አይነት መታየት እንደሌለበት ቢደነግግም፤ በሥራ ላይ ግን በተቃራኒው እየተተገበረ እንደሚገኝ የማሕበሩ ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ጌታቸው ለአሐዱ ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው፣ በተለያዩ አገራት ያለውን ልምድ ጠቅሰው ለጥብቅና ሙያ የሚሰጠው ከለላና የሙያው ጠርዝ እንዲከለል በማድረግ ረገድ በኢትዮጵያ ካለው የተለየ ነው ብለዋል።
አሐዱም ለጥብቅና ሙያ በልዩነት እንደሌላው ንግድ መታየት የለበትም የሚለውን የማሕበሩ ቅሬታ በማንሳት የማሕበሩን ፕሬዝዳንት የጠየቀ ሲሆን፤ በምላሻቸውም በኢትዮጵያ ያለው የንግድ ሕጉ ጭምር ቀደም ሲል እንደማይፈቅድ ተናግረዋል።
የጥብቅና ሙያ ከሌላው የንግድ አይነት በተለየ መልኩ ምርትና አገልግሎትን ማስተዋወቅ በንግድ ሕጉ የተከለከለ መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህ በእዲህ እንዳለ ንግድ ሥራ ፍቃድ በሚስጥበት ጊዜም ጠበቆች ማሕበራዊ ግልጋሎት እንዲሰጡ የሚያስገድድ አንቀጽ እንዳለው አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የጠበቆች ግብር ክፍያን በተመለከተ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲነሳበት እየተሰማ ነው ተብሏል።
ይሁንና ከዛሬ ነገ መፍትሔ ያገኛል ተብሎ እየተጠባበቁ እንደሆነ በመግለጽም፤ የሚመለከተው አካል ጉዳዮን በትኩረት እንዲመለከተው መጠየቁ ተነግሯል።
የገቢዎች ሚኒስተርና በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ማለትም የገንዘብ ሚኒስቴርና የፍትሕ ሚኒስቴር ጋር እየተመከረበት መሆኑን ገልጿል።
በቅርቡም መፍትሔ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳለው ጠቅሶ፤ በዋነኝነት ጉዳዩ ኢትዮጵያ በምትመራበት የንግድ ሕግ አንፃር የሚታይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መናገሩን ይታወሳል።
በአማኑዔል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አሐዱ ባንክ የጸጥታ ችግር እና የኢኮኖሚ አለመመጣጠን ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ገለጸ
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አሐዱ ባንክ በአገልግሎት ዘርፍ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚታየው ምቹ ያልሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ በአንዳንድ የሐገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉት የጸጥታ ችግሮችና የኢኮኖሚ አለመመጣጠን ጋር ተደማምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ተጽዕኖ እንዳደረሰበት አስታውቋል፡፡
ባንኩ በዛሬው ዕለት 3ኛ መደበኛ የባለ አክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን በሚሊኒየም አዳራሽ አከናውኗል፡፡
በጉባዔውም የባንኩ ዘርፍ ተለዋዋጭና ጥብቅ በሆነ መመሪያዎች ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ የገለጹት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ሰብስቤ፤ ለማሳያነት በነሐሴ 2016 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የናረውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር በማለም የንግድ ባንኮች በሚያበድሩት ብድር ላይ ጣሪያ ማስቀመጡን አስታውቀዋል፡፡
ይህ ፖሊሲ በባንኮቹ አፈጻጸምና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በሐብት ማንቀሳቀስ አቅም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ እንደነበረ ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም፤ ይህንን ፈታኝ ተግዳሮት በማለፍ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ የሚባል ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉና የበጀት ዓመቱን በስኬት ማጠናቀቁን አቶ አንተነህ ተናግረዋል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ በሪፖርታቸው ፤ አሐዱ ባንክ በዋና የፋይናንስ መለኪያዎች እድገት በማስመዝገብ የሚያስመሰግን ውጤት ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
የባንኩ ቅርንጫፍ ተደራሽነትን ወደ 104 ከፍ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በውጭ ምንዛሬ ረገድም 80 ነጥብ 1 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ የፋይናንስ ሁኔታ የተሻሻለ እንደነበር በመግለጽ በአሁኑ ወቅት የባንኩ አጠቃላይ ሐብት 6 ነጥብ 26ቢሊዮን መድረሱን አንስተዋል፡፡
የባንኩ የተፈጸመ የካፒታል መጠን ብር 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን መሆኑን አንስተው፤ አጠቃላይ የተከፈለ 1 ነጥብ 03 ቢሊዮን ማድረስ መቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት የሀገሪቷን የሚኒተሪ ፖሊሲ ለውጦችን በመከተል ተከታታይ ጥናቶችን በማካሔድ ከወቅቱ ጋር በተመጣጣነ መልኩ እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡
በአለምነው ሹሙ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የቱሪዝም ሚኒስቴር ላለፋት 15 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ፓሊሲ ማሻሻያ ሊያደርግ መሆኑን ገለጸ
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ለውጦችን ከዘርፉ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም በማለም ላለፋት 15 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ፓሊሲ ማሻሻያ ሊያደርግበት መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ የቱሪዝም ፓሊሲውን ክለሳ በተመለከተ ከግሉ ዘርፍ እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች ጋር ምክክር አድርጓል።
የኮሮና ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ያለው ተወዳዳሪነት እና ፓሊሲው የቀደመው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን መሠረት ያደረገ መሆኑ ፓሊሲውን ለመከለስ ምክንያት እንደሆነ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገልጸዋል።
ይህ ፓሊሲ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 15 ዓመታት ሲያገለግል መቆየቱን አንስተዋል። "ፓሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ ሂደትም ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ብቁ የሠው ሀይል በመኖሩ መልካም አጋጣሚ ነው" ብለዋል።
እንዲሁም በግል ዘርፍ የተሠማሩ ባለሀብቶችም ተሳታፊ መሆናቸውና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገነቡ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች መስፋፋታቸውን ገልጸዋል።
አሁን በሥራ ላይ ያለው ፓሊሲ የራሱ የሆኑ በጎና አሉታዊ ጎኖች አሉት የተባለ ሲሆን፤ ፓሊሲው የሚፈለገው ግብዓቶች ከተካተቱበት በኋላ ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብ መሆኑን ዶ/ር የዚህዓለም ሲሳይ ተናግረዋል።
"ፓሊሲው ድህነትን በማስወገድ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ሁነቶችን በመጠበቅ ረገድ የራሱን ሚና ቢጫወትም የጎብኚዎች ቁጥር በሚፈለገው ልክ አለመጨመር፣ መዳረሻዎችን ለማስፋት ውስንነት እና አለም ከቀፍ ተደራሽነት ዝቅተኛ ነበር" ብለዋል።
በተመሳሳይም የቴክኖሎጂ፣ የቅርስ ጥበቃ፣ የአደጋ እና ቅድመ መከላከል አማራጭ መንገዶች ፓሊሲዉ ያልተመለከታቸው እንዲሁም ግልጽ መመሪያዎችን ያላስቀመጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በሚከለሰው አዲሱ ፖሊሲ ሰፊ የሥራ እድል የውጭ ምንዛሬ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት የአገልግሎት ጥራት ቅርሶቸን በአግባቡ መጠበቅ እንዲሁም የአፈጻጸም ክፈተቶችን ለመሙላት አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ጨምሮ የሚመለከት እንደሚሆን አንስተዋል።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከ2 ሺሕ በላይ ተማሪዎች አስመረቀ
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺሕ 811 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በሀውልቲ ሰማዕታት አዳራሽ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው ያስመረቀው በህክምና፣ በምህንድስና፣ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ተማሪዎችን ሲሆን፤ 1 ሺሕ 950ዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ ቀሪዎቹ ደግሞ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።
በተጨማሪም ዩንቨርስቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 28 በመቶዎቹ ሴት ተማሪዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከድህረ ጦርነቱ በኃላ ለሁለተኛ ጊዜ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ዘንድሮ በአንደኛ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብር ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ ይህ ለ30ኛ ጊዜ ነው፡፡
በዘንድሮ የትምህርት ዓመት 2 ሺሕ 800 አዳዲስ ተማሪዎች ወደ ዩንቨርስቲዉ የተመደቡ ሲሆን፤ በመጪው ጥር ወር አዲስ ለተመደቡ ተማሪዎቹች ጥሪ የማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በውሃ እጥረት ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጥን ነው ሲሉ የሆለታ ከተማ ኗሪዎች ገለጹ
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል ሆለታ ከተማ ጎጥ 8 አካባቢ ውሃ ከጠፋ ከ3 ወር በላይ እንደሆነና በውሃ እጥረት እንደተቸገሩ ነዋሪዎች ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ለወራት በተቋረጠው የውሃ አቅርቦት ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጡ መሆኑንም ኗሪዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ውሃ ከሰኔ ወር ጀምሮ በመቋረጡ ምክንያት ለመጠጥና ምግብ ለማብሰል እንዲሁም ለንጽህና መጠበቂያ ባለማግኘታቸው ለጉንፋንና መሰል በሽታዎች እየተጋለጡ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
በተለይም በችግሩ በአካባቢው የሚኖሩ አቅመ ደካሞች የበለጠ ተጎጂ እንደሁኑ የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ወጣቶች ከሌላ አካባቢዎች እያመጡ ለመርዳት ቢሞክሩም በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሆለታ ከተማ ጎጥ 8 አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች ከሌላ ቦታ ተፈናቅለው የመጡ ደካሞች የሚበዙበት በመሆኑ ችግሩን መቋቋም እንዳቃታቸውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝ በአካባቢው የሚመለከተውን አካል በተደጋጋሚ ቢጠይቁም የሚሰጣቸው ምላሽ፤ “ክረምቱ ጭቃ ስለሆነ ለመስራት ተቸግረናል” የሚል ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም "ከክረምት ከተጠናቀቀ በኋላም ያለው የውሃ ችግር እንዲፈታ ስንጠይቅ ደግሞ፤ ማሽን ተበላሽቷል የሚል መልስ ነው የሚሰጠን" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ አሐዱ የሆለታ ከተማ የውሃና ልማት ጽ/ቤት ምላሽ እንዲሰጥበት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ምላሹን ባገኘን አፍታም ወደ እናንተ እናቀርባለን፡፡
በአለምነው ሹሙ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
#አሐዱ_ትንታኔ
ሄዝቦላህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴልቪቭ የሚገኘው የእስራኤል ጦር ሰፍር በሰው አለባ ድሮን መደብደብ መጀመሩን አስታውቋል። የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በቴላቪቭ የሚገኘውን የእስራኤል ግዙፍ የጦር ሰፍር መደብደቡንም ገልጿል፡፡
የቡድኑ ጥቃት ከእስራኤል የአየር መከላከያ "አይረደም" ቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል። ጥቃቱን አስመልክታ እስራኤል ምላሽ ሰጥታለች፡፡ እነዚህን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በዛሬው የአለም አቀፍ ትንታኔያችን ተመልክተነዋል፡፡
ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/MVu7_16OyU0?si=d9r6Nbly6VDrxn-0
በአማራና ኦሮሚያ ክልል ያለው ማህበረሰብ በመንግሥትና ታጣቂ ሃይሎች መካከል ሆኖ ዋጋ እየከፈለ ነው ሲሉ ፓርቲዎች ገለጹ
ጥቅምት 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራና እና ኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ሃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ባለው ግጭት ህብረተሰቡ ዋጋ እየከፈለ ነው ሲሉ ከአሐዱ መድረክ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል።
" 'የቀን ገዢና የማታ ገዢ' በሚል ህብረተሰቡ እየሞተ ነው" ያሉት ፖለቲከኛና የእናት ፓርቲ አባል የሆኑት ጌትነት ወርቁ፤ "በተለይም በኦሮሚያ ክልል ችግሩ የጎላ ነው" ይላሉ።
"በተመሳሳይም በአማራ ክልል የተሟላ ጦርነት እየተካሄደ ነው" ያሉ ሲሆን፤ በመጠኑና በአይነቱ ከሌሎች ጦርነቶች የሚለየበት ሁኔታ ስለመኖሩም ተናግረዋል።
"በሁለቱም ክልሎች ያለው ሁኔታ የሚገለፅበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም፤ የመፍትሔ ሃሳቦች ግን ሁሉንም ሊያስማሙ ይችላሉ" ያሉት ፖለቲከኛ ጌትነት፤ በእነዚህ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙም አንስተዋል።
"መንግሥት 'አደረኩ' ያላቸው ጥረቶች የሚበረታቱ ቢሆኑም 'እንነጋገር' ማለት 'ተማረኩልኝ' ማለት ነው" ሲሉ ገልጸው፤ ገለልተኛ የአፍሪካ ሀገራት ባሉበት ድርድር መደረግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
"ግጭቶች እያደጉና እየሰፉ የዜጎች ችግርና ሰቆቃ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ መቋጫው የት ነው የሚለው የእኛም ጥያቄ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ የአዲስ አበባ ኮሚቴ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አበበ አካሉ ናቸው።
"የመንግሥት የመጀመሪያ ኃላፊነት የሀገርና ሕዝብን ደህንነትን ማስጠበቅ ቢሆንም፤ ይኼን ማድረግ ግን አልቻለም" ሲሉ ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለጹት፡፡
አክለውም "በጠብመንጃ የሚመጣ ሰላም ዘላቂነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው" ብለዋል።
በዚህም በሁለቱ ክልሎች የተፈጠሩ ግጭቶችን መነሻ ማጤን እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን፤ "መንግሥት በራሱ መዋቅር ውስጥ ያሉ ችግሮችን መፈተሽ ይገባዋል" ባይ ናቸው።
አክለውም፤ "የሰላም እና የጸጥታ ጉዳይ ሁሌም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጥያቄ መልክ የሚነሳ ቢሆንም የሚመለሰው መልስ አጥጋቢ አለመሆንና መሬት ላይ ወርዶ የተሰራ ሥራና ውጤት ግን የለም" ብለዋል።
ከአሐዱ ጋር ቆይታ ያደረጉ ፖለቲከኞች፤ መንግሥት በክልሎቹ ያለውን ችግር በማመን ለሀቀኛ ድርድር በመቀመጥ የዜጎችን ችግር ሊፈታ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተውበታል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታን "ሾተላይ" ሲሉ መግለጻቸው አይዘነጋም።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የሸበሌ ወንዝ ሙላት በሶማሊ ክልል ሦስት ወረዳዎች የንብረት ውድመት አደረሰ
ጥቅምት 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሸበሌ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት በሶማሊ ክልል ሸበሌ ዞን ሥር በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች የንብረት ውድመት ማድረሱ ተገልጿል።
የጎርፍ አደጋው በሸበሌ ዞን ቀላፎ፣ ሙስታሂልና ፌርፌር ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ በተለይም በቀላፎ ወረዳ ባሉ ሰባት ቀበሌዎች በንብረት እና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ ሚዲያ ዘግቧል።
አደጋውን ተከትሎ በአከባቢው የሚኖሩ ዜጎች በአንስተኛ ጀልባዎች ቦታውን ለቀው እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን በጎርፉ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የተጎዱ ነዋሪዎችን ለማገዝ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የሸበሌ ወንዝ ሙላት በተደጋጋሚ በሸበሌ ዞን ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ በነሐሴ ወር 2016 በተመሳሳይ ወረዳዎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ ሁለት ሺሕ 827 አባወራዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ፤ 6 ሺሕ 186 ሄክታር የሰብል መሬት ላይ ጉዳት ማድረስ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሦስት ወራት ውስጥ በተከሰቱ 127 አደጋዎች 93 ነጥብ 6 ሚልዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለጸ
👉በአደጋዎቹ የ22 ሰዎች ሕይወት አልፏል
ጥቅምት 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 ዓ.ም. ብቻ ባጋጠሙ 127 አደጋዎች 93 ነጥብ 6 ሚልዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን እና የ22 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ከደረሱት አደጋዎች 117ቱ በአዲስ አበባ ቀሪዎቹ 10 አደጋዎች ደግሞ በሸገር ከተማ ያገጠሙ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለአሐዱ በሰጡት መረጃ እንዳሉት፤ ካጋጠሙት አደጋዎች መካከል 63ቱ የእሳት ቃጠሎ፣ 28ቱ የጎርፍ፣ 18ቱ የንግድ ቤቶች ቃጠሎዎች ሲሆኑ 64ቱ ደግሞ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው፡፡
በደረሱት አደጋዎች ምክንያት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን ጨምሮ 12 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡
የደረሱትን አደጋዎች ለመቆጣጣር በተደረገ ርብርብ በአደጋ ውስጥ የነበሩ 72 ሰዎችን እና 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማትረፍ መቻሉንም የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ተናግረዋል፡፡
አሁን ያለው ደረቅና ነፋሻማ አየር ድንገተኛ የእሳት አደጋን በማባባስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚያበረክት ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በእመቤት ሲሳይ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
472 ሺሕ 500 ኩንታል ዩሪያ የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ ጂቡቲ ወደብ ደርሳለች
ጥቅምት 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017/18 የምርት ዘመን ከውጭ ከሚገዛው 23 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ፤ 472 ሺሕ 500 ኩንታል ዩሪያ የጫነች የመጀመሪያዋ ኤም ቪ አባይ ሁለት የተሰኘች የኢትዮጵያ መርከብ ጂቡቲ ወደብ መድረሷ ተገልጿል።
በቀጣይ ቀናትም ተጨማሪ ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርሱ እና ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ ሥራውም በፍጥነት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም ለ2017/18 የምርት ዘመን ለሚውል 23 ሚሊየን ኩንታል ዩሪያ እና ዳፕ የአፈር ማዳበሪ ግዥ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በመንግሥት መፈቀዱ ይታወሳል።
መንግሥት በአፈር ማዳበሪያ ግዥ ላይ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ አዲስ የግዥ መመሪያ በማውጣቱ እና ከግዥ ጋር የተያያዙ ችግሮች በመፈታታቸው ባለፈው የምርት ዘመን 21 ቢሊየን ብር ለማዳን መቻሉንም ኮርፖሬሽኑ ገልጿል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
#አሐዱ_ወቅታዊ
የኮሪደር ልማቱ እና የማህበረሰቡ ቅሬታ!
አሐዱ በልማት ተነሽነት የተፈናቀሉ፣ "የቀበሌ ቤት ኗሪ ነን" ያሉ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በአንድ የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የሚኖሩ የበርካታ እናቶች እና ሕጻናትን ቅሬታ ተቀብሎ እንደሚከተለው አጠናክሮታል።
ሙሉ ጥንቅሩን ለመከታተል ከሥር ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ!
👇
https://youtu.be/5RbrC0WiTIQ?si=2O09epRr7g9Sgzx6
"መንግሥታዊ ስልጣን ማን ይያዝ? የሚለው ጉዳይ በየትኛውም መመዘኛ ወደ ድርድር የማይቀርብ ነው" የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር
ሕዳር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መንግሥታዊ ስልጣን ማን ይያዝ? በሚል የስልጣን ክፍፍል ጉዳይ በየትኛውም መመዘኛ ወደ ድርድር የማይቀርብ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህወሓት የመንግሥት ሥራዎችን ከማደናቀፍ አልፎ ይፋዊ የመፈንቅለ መንግሥትን ወደ መፈፀምና ፍፁም ስርዓት አልበኝት ወደ ማስፋፋት መሸጋገሩን ዛሬ ሕዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
በመግለጫውም፤ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በውድ መስዋትነት የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠበቅ የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ይሁን እንጂ በህወሓት ከፍተኛ አመራር መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትና ከነሐሴ 2016 ጀምሮ በግልፅ እየታየ የሚመጣውን ልዩነት፤ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ከባድ እንቅፋት እንደፈጠረበት አስታውቋል።
"በአንድ በኩል ይህ ልዩነት ከጊዜ ወደጊዜ እየተካረረ እንዲሄድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራዎች በተደራጀ መንገድ እንዲደናቀፉ በማድረግ የመንግሥት ሥራዎችን የማሰናከል የተቀናጀ ሥራ ሲከናወንም ቆይቷል፤ አሁንም እንደቀጠለ ነው።" ሲልም በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራውን የህወሓት ቡድን ከሷል።
ይህን ዘመቻ ሕጋዊ ያልሆነ ጉባኤ ባካሄደው ህወሓት በበላይነት የሚመራ መሆኑን የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ "ህዝባችን ተስፋ እንዲቆርጥና በቀጣይ አዙሪት እንዲጠመድ ሆን ተብሎ የሚደረግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው።" ብሏል።
"በቅርቡ ደግሞ ይህ ቡድን የመንግሥት ሥራዎችን ከማደናቀፍ አልፎ ይፋዊ የመፈንቅለ መንግሥትን ወደ መፈፀምና ፍፁም ስርዓት አልበኝት ወደ ማስፋፋት ተሸጋግሯል" በማለትም ከሷል።
ለዚህም በመቐለ ከተማ፤ ሰሜን ምዕራብና ማዕከላዊ ዞኖች እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ማረጋገጫ አብነቶች መሆናቸውን አመላክቷል።
"ካለፉት 2 ሳምንታት ወዲህ ደግሞ 'ከትግራይ ሰራዊት አመራሮች ጋር ተረዳደተናል፤ ከላይ እስከ ታች የመንግሥት መዋቅሩን ለመቆጣጠር ጨርሰናል' እያለ ሰፊ የማደናገር ተግባር ላይ ተጠምዷል።" ያለው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ "ይህ አገላለፅ ራሱን በራሱን የሚያታልልበትና የሚያሞኝበት አጉል ተስፋ ከመሆን አልፎ ጠብ የሚል ሃቅ የሌለው መሆኑ ግን መታወቅ አለበት።" ብሏል።
አክሎም፤ "ይህ ቡድን ከስልጣኑ ዉጭ ሊያስብና ሊያልም ስለማይችል፤ በየእለቱ ስልጣን የሚይዝበትን ህልም በማለም፤ ለስልጣን ሲል ሁሉንም ዓይነት ጥፋት ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይል በተደጋጋሚ እየታየ መጥቷል።" ሲል ገልጿል።
"ከሰራዊቱ ጋር ተግባብተናል በሚል እያደረጋቸው ያሉ ተደጋጋሚ ማደናገሪያዎችም ቢሆኑ ለስልጣን ሲባል ለትግራይ ህዝብ ህልውና የቆመን ሰራዊት ጭምር ለጠባብ ፍላጎቱ ማሟያ ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይል በሚገባ የሚያሳይ ድርጊት ነው።" በማለትም የህወሓትን እንቅስቃሴ ኮንኗል።
በተጨማሪም ህወሓት፤ በሰራዊት አመራሩም ሆነ በሃይማኖት አባቶች የተጀማመሩ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ሂደቶች ከልብ እንደማይቀበልም በአደባባይ እየገለጸ መምጣቱንም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታውቋል።
ህወሓትን ለማዳን በሚደረግ ትግል በጊዜያዊ አስተዳደሩ ዉስጥ የሚገኙ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች የሚቻላችውን ሁሉ ለመድረግ ዝግጁ መሆናችውን የገለጸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ ከማንኛውም አካል ጋርም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገርም ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጫው አስታውቋል።
ነገር ግን "መንግሥታዊ ስልጣን ማን ይያዝ? በሚል የስልጣን ክፍፍል ጉዳይ ላይ ግን በየትኛውም መመዘኛ ወደ ድርድር የማይቀርብ መሆኑን ግልፅ መሆን አለበት።" ሲል አሳስቧል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠበቅ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በሚከናወነው ትግል በሃገር ዉሰጥና በውጭ የሚገኘው መላው ሕዝብ ከጎኑ እንዲሆንም ጥሪ አቅርቧል።
ከዚህ ቀደም በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለመፍታት፤ አርብ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን ያገናኘ የምክክር መድረክ በትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አባቶች አማካኝነት ተዘጋጅቶ ሁለቱ አካላት ተገናኝተው መወያየታቸውን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል።
ነገር ግን ውይይቱን ተከትሎ በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) "ከብፁአን የሃይማኖት አባቶች ተግሳፅና ምክር የዘለለ ውጤት የሌለው ነው" ሲል መግለጹ ይታወሳል።
አክሎም በተለያዩ አካላት እና ሚዲያዎች ሁለቱ አካላት "ለእርቅና ሽምግልና ተስማምተዋል" በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው።" ሲል አስታውቆ ነበር።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የጎግል ፕሌይ አልሚዎች ምዝገባ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል መጀመሩ ተገለጸ
ሕዳር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጎግል ፕሌይ የአልሚዎች ምዝገባ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል መጀመሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ ምዕራፍ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ባለቤቶች መተግበሪያዎቻቸውን በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ ዲጂታል መድረኮች ላይ እንዲያትሙ አዲስ ዕድሎችን እንደሚከፍት ተመላክቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ መንግሥት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት በርካታ ተነሳሽነቶችን በመተግበር እየሰራ መሆኑን ገልጸው "ይህ አዲስ ጅማሮ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ነው" ብለዋል።
"የጎግል ፕሌይ የአልሚዎች ምዝገባ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል መጀመሩ ለኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
አክለውም፤ ይህንን ዕድል ተጠቅመው የዘርፉ ባለሙያዎች ችግር ፈቺ መተግበርያዎችን በማልማት በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በሚኒስቴሩ አማካሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያውያን ጀማሪ ኩባንያዎች (ስታርታፖች) ምቹ ሥነ-ምህዳርን ለማዳበር ከሚተገበሩ ሥራዎች መካከል፣ በአለም አቀፍ የዲጂታል መድረኮች እንዲሳተፉ የሚያስችሉ አለማቀፋዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር ወሳኝ በመሆኑ ዕድሉን ለማመቻቸት የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አያይዘውም "ይህ አዲስ ዕድል ኢትዮጵያውያን ገንቢዎች የGoogle Playን አለምአቀፍ ታዳሚዎች በቀጥታ በማስገኘት መተግበሪያዎቻቸው ሰፊ እይታን እንዲያገኝ እና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችላል" ብለዋል።
ይህ አዲስ ዕድል የሀገር ውስጥ ገንቢዎችን በማበረታታት ከአካባቢው፣ ከማህበረሰቡ ወግና አኗኗር ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን መተግበሪያዎች በማልማት እንዲሁም፤ ለአለማቀፍ ገበያው የሚመጥን ሥራ ለመስራት አቅም ያላቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያበረታታ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኦንላይን የሚፈጠሩ ማጭበርበሮችን መቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስልክ እየደወሉ እንዲሁም የተለያዩ የኦን ላይን ዘዴዎችን ተጠቅመው ከደንበኞች ላይ የሚያጭበረብሩ ግለሰቦችን አግኝቶ እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ እንደሆነበት ገልጿል፡፡
የተፈጠረው ችግር በራሱ በደንበኛው ነው ውይንስ በሌላ አካል ነው የሚለውን ለመለየት የሚያስቸግር በመሆኑ፤ በህግ ለማስጠየቅም ከፍተኛ ችግር እየፈጠረበት መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡
በዚሁ ዙሪያ ለሚፈጠሩ የኦን ላይን ማጭበርበሮች ጥፋት ተጠያቂ ለማድረግ በኢትዮጵያ ሕግ ባለመኖሩም ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተነስቷል።
"በመሆኑም ይህንን በሚመለከት ከህግ አውጪዎች ጋር ውይይት በማድረግ በህግ ማዕቀፍ ለማስገባት እየተሰራ ነው" ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የባንኩ የኢንፎርሜሽን ሲስትም ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አማረ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ከፖሊስ እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ጋር በመሆን መረጃዎችን ተንትኖ አጥፊዎችን ለማጋለጥ እየሰራ እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በአብዛኛው የሚፈጠሩ ወንጀሎች የሚፈፀሙት ደንበኛው ካለው የመረጃ እጥረት የተነሳ በመሆኑ ይህንን ችግር ለመፍታት በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሰራን እንገኛለን ሲሉም አቶ አማረ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
#አሐዱ_መድረክ
"ፓርላማ ላይ መልስ መስጠት ለሀገር ሰላም አያስገኝም"
ሙሉ ቆይታውን ለመከታተል ከሥር ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ!
👇
https://youtu.be/exin1vDw-Ss?si=uCqWfGtmlIq3oZ-P
ነዋሪ ያልገባባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ውል ለማቋረጥ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ እስከ ሕዳር 30 ተራዘመ
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በተለያዩ ጊዜያት በእጣ እና በጨረታ ተላልፈው ነዋሪ ያልገባባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ውል ለማቋረጥ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ እስከ ሕዳር 30 ቀን 2017 ድረስ ማራዘሙ አስታውቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የቤት ባለቤቶቹ ወደ ቤታቸው የማይገቡ ከሆነ በሕግ አግባብ ውል የሚቋረጥ መሆኑን ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡
በዚሁ አግባብ በርካታ የቤት ባለቤቶች ወደ ቤታቸው የገቡ ወይም ለመግባት ዕድሳት ላይ ስለመሆናቸው ባደረገው የአካል ምልከታ መገንዘቡን የገለጸ ሲሆን፤ አሁንም አንዳንድ የቤት ባለቤቶች ወደ ቤታቸው ለመግባት ምንም እንቅስቃሴ ያላደረጉ በመሆኑ በውል ተላልፈው ነዋሪ ያልገባባቸው ቤቶች እንዳሉ መለየቱን አመላክቷል፡፡
በመሆኑም የኮርፖሬሽኑን ጥሪ ተቀብለው ቤታቸውን አድሰው ለመግባት የጊዜ እጥረት ያጋጠማቸው አንዳንድ የቤት ባለቤቶች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ማራዘም አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት እስካሁን ድረስ ወደቤታቸው ለመግባት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ያላደረጉ እንዲሁም ቤት ለማደስ የጊዜ እጥረት ያጋጠማቸው የቤት ባለቤቶች እስከ ሕዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ለመጨራሻ ጊዜ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማይገቡ ነዋሪዎች የሽያጭ ውላቸው የሚቋረጥ እና በቤታቸው ውስጥ ለሚፈጸም ማንኛውም ሕገወጥ ድርጊት ተጠያቂ የሚሆኑ መሆኑንም ኮርፖሬሽኑ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ወጋገን ባንክ በበጀት ዓመቱ ትርፍ በትርፍ ሆኟለሁ አለ
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ወጋገን ባንክ በበጀት ዓመቱ 9 ነጥብ 8 ቢልየን ብር የተጣራ ገቢ ማግኘቱን ለአክስዮን ባለ ድርሻዎች እወቁልኝ ብሏል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ካለፉት በጀት ዓመታት ከፍተኛው ትርፍ መሆኑን በዛሬው ዕለት ባካሄደው የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ገልጿል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከር በ40 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ገልጿል።
ባንኩ ያገኘው ትርፍ በታሪኩ ከፍተኛውን መሆኑን ጠቅሶ፤ የትርፍ መጠኑንና የአክስዮን አባላቱ ቁጥር እያደገ መሆኑን ተናግሯል።
የአንድ አክስዮን ትርፉ ወደ 36 ነጥብ 9 በመቶ አድጎለታል ተብሏል።
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 27 በመቶ እድገት ማሳየቱንና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 5 ነጥብ 1 ቢልየን ብር መድረሱን የገለጸ ሲሆን፤ ይህም ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ካስቀመጠው የባንኮች አነስተኛ ካፒታል መስፈርት በላይ መሆኑን ለአክስዮን ባለድርሻዎች አስታውቋል።
በበጀት ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ የ22 በመቶ እድገት በማስመዝገብ 52 ነጥብ 1 ቢልየን ብር መድረሱንም ጠቅሷል።
ባለአክስዮኖች ብዛትም በ12 ሺሕ ያህል እንዳደገለት የገለጸም ሲሆን፤ ባንኩ ከዚህ ቀደም የገጠሙትን ችግሮች በመቅረፍ ወደ ተሻለ ደረጃ የትርፍ መጠኑን ማድረሱን ገልጿል።
በአማኑዔል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
"የደመወዝ ማስተካከያው የጥቅምት ወር ክፍያን ታሳቢ በማድረግ ይከፈላል" የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር)
ጥቅምት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ የጥቅምት ወር ክፍያን ታሳቢ በማድረግ እንደሚከፈል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኮሚሽነሩ በማህበራዊ ትስስት ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ "የተፈቀደው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ ዘግይቷል፣ ቀርቷል የሚሉ ሃሳቦች እየተራመዱ ነው። በሲቪል ሰርቪስ በኩል የሚለቀቁ መረጃዎች ኦፊሴላዊና የሚተገበሩ መሆኑን መተማመን ጥሩ ነው።" ብለዋል፡፡
አክለውም፤ ቀደም ሲል የመንግሥት ሰራተኞችን የደመወዝ ስኬል በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚናፈሱ አሳሳች ወሬዎች ማህረሰቡ እንዳይሳሳት መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የተጨማሪ ክፍያ በጀቱን ለሚመለከታቸው ተቋማት መፍቀዱን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ "በእኛ መስሪያ ቤትም በኩል የተስተካከለውን የጥቅምት ወር ደመወዝ ተከፍሏል። ሌሎችም እንደዚሁ የከፈሉ አሉ።" ብለዋል
የቀሩት ተቋማት ደግሞ ማስተካከያውን ለማድረግ የማጥራት ሥራ እየሰሩ ሊሆን እንደሚችል ያመላከቱም ሲሆን፤ "እነዚያም ዝግጅታቸውን ሲያጠናቅቁ የተስተካከለው የጥቅምት ወር ክፍያ ታሳቢ በማድረግ የሚከፍሉ ይሆናል።" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ ጥቅምት 09/2017 ዓ. ም በሰጡት ማብራሪያ አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው ነበር።
በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፤ ለደሞዝ ጭማሪው 91 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጸው፤ ክፍያው ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በጠበቆች ላይ እየተጣለ ያለውን የግብር አከፋፈል ቅሬታ የሚከታተል ኮሚቴ መቋቋሙ ተገለጸ
ጥቅምት 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከዚህ በፊት በጠበቆች ላይ በሚጣለው ግብር ቅሬታ እንዳለ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፤ የፌደራል ጠበቆች ማሕበር አሁን ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን የሚከታተል ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጿል።
የተቋቋመው ኮሚቴ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መስርያ ቤቶች የተውጣጡ አባላትን የያዘ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በዚህም በጠበቆች ላይ እየተጣለ ካለው ግብር ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ እልባት ያገኛል የሚል እምነት መኖሩን፤ የፌደራል ጠበቆች ማሕበር ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ጌታቸው ለአሐዱ ገልጸዋል።
ማሕበሩ በተለያዩ ጊዜያቶች ጥያቄውን ሲያቀርብ የነበረ ቢሆንም ከመንግሥት ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።
የጥብቅና ሥራ ከፍትህ ስርአቱ ጋር የሚገናኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ አገር ጥሩ የሚባል ልምምድ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።
እየቀረበ ያለውን ጥያቄ የገቢዎች ሚኒስቴርን ጨምሮ የፍትሕ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንዲያጤኑ ማሕበሩ ሐሳብ ማቅረቡንም ፕሬዝዳንቱ አክለው ተናግረዋል፡፡
ማሕበሩ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ማቅረብ ከጀመረ ከሁለት ዓመታት በላይ እንደሆነው የገለጸም ሲሆን፤ ይሁን እንጂ እስካሁን ከመንግሥት የተሰጠ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ አስታውቋል።
በአማኑዔል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የገንዘብ ሚኒስቴር የፍራንኮ ቫሉታ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተፈቅደው የነበሩ ምርቶች ፍቃድ መሰረዙን አስታወቀ
ጥቅምት 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔውን ያሳለፈው መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተከትሎ የዋጋ ግሽበት እንዳይከሰት በሚል እንደነበር የገለጸ ሲሆን፤ አሁን ላይ ዋነኛውን ምእራፍ የታለፈ በመሆኑ ፍቃዱን አንስቻለሁ ብሏል።
ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተፈቅደው የነበሩ የምግብና የፋብሪካ ግብአት የሚውሉ የውጭ ምርቶች መሆናቸውን አሐዱ በሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤ ላይ ተመልክቷል።
የፍራንኮ ቫሉታ ፍቃዱን ከጥቅምት 29/2017 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ የማይደረግ መሆኑን ለጉምሩክ ኮሚሽን አባሪ አድርጎ በላከው ደብዳቤ ላይ ተገልጿል።
መንግሥት የተሟላ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉንና ወደ ከፍተኛ ምእራፍ እየተሸጋገረ በመሆኑን ገልጾ፤ ኢኮኖሚው መልካም ውጤቶች የታየበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በተመለከተ በኢትዮጵያ ያሉ ንግድ ባንኮች በቂ የሚባል የውጭ ምንዛሪ በበቂ ሁኔታ እየቀየረ ስለመሆነ ከእንግዲህ በኃላ ፍራንኮቫሉታ የሚባል ነገር እንደማይኖር የገንዘብ ሚኒስቴር በሚኒስቴሩ አሕመድ ሺዴ ተፈርሞ የወጣን ደብዳቤ ያሳወቀው።
በአማኑዔል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢንቨስትመንት ባንክ ዘርፍ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ወደ ፋይናንስ ገበያው እንዲገቡ መንግሥት ግፊት ሊያደርግ ይገባል ተባለ
ጥቅምት 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርአት የንግድ ባንኮች ተፅእኖ የሚስተዋልበት በመሆኑ ዘርፉ ሌላ አማራጭ መመልከት ይኖርበታል ሲሉ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪዎች ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን "በኢንቨስትመንት ባንክ መቋቋም የሚሹ ኩባንያዎቹ በሩን ክፍት አድርጌያለሁ" ቢልም እስካሁን የተቋቋሙ የኢንቨስትመንት ባንኮች አለመኖራቸውን፤ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ያሬድ ኃይለመስቀል ለአሐዱ ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ባንኮች ለፋይናንስ ስርአቱ መረጋጋትና መነቃቃት የሚሰጡት ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ነው አማካሪው የገለጹት።
የኢንቨስትመንት ባንኮች ለባንክ ስርአት ውጤታማነትና ቅልጥፍና የሚሰጡት ጥቅም በሌሎች አገራት ያለውን ልምድ የጠቀሱት አቶ ያሬድ፤ "በዘርፉ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ፋይናንስ ገበያ እንዲገቡ መንግሥት ግፊት ሊያደርግ ይገባል" ብለዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ያሉ ንግድ ባንኮች የሚከተሏቸው አንድ ሕጎች ለንግዱ ዘርፍ አመቺ እንዳልሆኑ የሚናገሩት ሌላኛው በዚሁ ዙርያ ያነጋገርናቸው የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ ከፈለኝ ኃይሉ ናቸው።
በኢትዮጵያ ያለውን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ አሁን ካለው ለውጥ በላይ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አማካሪዎቹ ለአሐዱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ 32 ንግድ ባንኮች፣ 1 ልማት ባንክ፣ 18 ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ እና 64 ማይክሮፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ ገበያውን እያቀለጣጠፉት ይገኛል ተብሏል።
በአማኑዔል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኢትዮጵያን ማጥቃት የሚፈልግ ማንኛውም አካል መጀመሪያ የሚያጠቃው ንግድ ባንክን ነው ተባለ
ጥቅምት 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ለሳይበር ጥቃት ከትናንሽ ተቋማት ይልቅ ትልቅ ተቋማት ተጋላጭ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ተናግረዋል።
"ትልቅ ተቋማት በቀላሉ ለመጠቃት ይዳረጋሉ" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ "በዚህም ኢትዮጵያን በሳይበር ጥቃት ሊፈፅም የሚያስብ ማንኛውም አካል በቅድሚያ የሚያጠቃው የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ነው" ብለዋል።
"አዲስ አበባን ለማጥቃት የሚፈልግ አካል መጀመሪያ ሊያጠቃ የሚችለው የንግድ ባንክ ሕንፃን ነው፡፡ ምክንያቱም ትልቅ በመሆኑ" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።
"በመሆኑም ተጋላጭ መሆናችንን በመገንዘብ በቂ የሳይበር ደህንነት ሥራዎችን ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል።
አክለውም "በዲጂታል ዓለም ትንሽ ስህተት ብዙ አደጋ እንደሚያደርስ ባለፈው ዓመት በሲስተም ብልሽት የተፈጠረው ነገር ማሳያ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህም መማር እንደሚያስፈል ተናግረዋል።
የሳይበር ጥቃት በዓለም ላይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይም የፋይናንስ ዘርፍ ደግሞ ይበልጥ ተጋላጭ መሆኑም ተነስቷል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በባንኩ የሲስተም ስህተት ምክንያት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማጣቱን መግለፁ አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርብ ጊዜያት ከደረሰበት 11 ሺሕ በላይ የሳይበር ጥቃት ላይ ሙሉ ለሙሉ ማክሸፍን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
በአቤል ደጀኔ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚገቡ ሰልጣኞች ቁጥር መሻሻል ማሳየቱ ተነገረ
👉 በተያዘው ዓመት ከአምስት ሚልየን በላይ ሰልጣኞች መመዝገባቸው ተገልጿል
ጥቅምት 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ባለፈው ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተናን ወስደው ውጤት ባለማምጣታቸው፤ ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚገቡ ሰልጣኞች በቁጥር ደረጃ መሻሻል መታየቱን ተነግሯል።
ቴክኒክና ሙያ ስልጠና የትምህርት ተቋማት ካላቸው ዝግጁነት አንፃር የሰልጣኞች ቁጥር የመቀነስ አዝማሚያ ሲስተዋልባቸው የቆየ ቢሆንም፤ አሁን ላይ የመሻሻል ሁኔታዎች መታየታቸው ነው የተገለጸው።
በዚህም መሠረት በተያዘው በጀት ዓመት ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሰልጣኞች ተቀብለው እያስተናገዱ መሆናቸውን የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ለአሐዱ አስታውቋል።
በቅርቡ ፀድቆ ሥራ ላይ በዋለው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የትምህርት ተቋማት አዋጅ መሠረት ማሻሻያ የተደረገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የገለጹት፤ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ከድር ናቸው።
በዚህም መሰረት የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመርያዎች መዘጋጀታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው፤ በኢትዮጵያ ያሉ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የትምህርት ተቋማት የተጣለባቸው ሐላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰው ሀብት ልማትና የሙያ ብቃት ላይ በብርቱ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከአምስት ሚልየን በላይ ሰልጣኞች መመዝገባቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ለዚህም የፌደራሉ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የአዋጁ ተፈፃሚነት በብርቱ እየተከታተለ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ለአሐዱ አብራርተዋል።
የቴክኒክና ሙያ የትምህርት ተቋማት ከዚህ በቀደሙ ዓመታት ሰልጣኞችን የመቀበል አቅማቸው ከፍተኛ እንደነበር ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም በታለመለት ልክ ሰልጣኞችን ማግኘት እየቻሉ እንዳልነበር ጠቅሰዋል።
ይሁንና ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ባካሄደዳቸው አንዳንድ ለውጦች ምክንያት አሁን ላይ ወደ ቀደመው ዝናው የመመለስ ጥረቶች እየተሳኩለት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ሲናገሩ ሰምተናል።
በአማኑዔል ክንደያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ