#የአሐዱ_መልህቅ
ጥንቅሩን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/Rm66EQghEU8?si=10lx-W0jqLdPIbSk
የዓመቱን ጤና መድኅን ክፍያ ካደስን በኋላ በድጋሚ ተጨማሪ ክፍያ መጠየቃችን አግባብ አይደለም ሲሉ ተጠቃሚዎች ተናገሩ
ጥቅምት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) “ዓመታዊ የጤና መድኅን መታወቂያ እድሳት ካከናወንን በኋላ ተጨማሪ ክፍያ ተጠይቀናል” ሲሉ ለአሐዱ የተናገሩት የጤና መድኅን ተጠቃሚዎቹ፤ "የዚህ ዓመቱ ክፍያ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ500 ብር ብልጫ እንዲኖረው ሲደረግ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠን ይገባ ነበር" ብለዋል፡፡
መታወቂያቸውን አድሰው ከተመለሱ በኋላ ስልክ ተደውሎ ጭማሪ እንደተደረገና በፍጥነት ቀርበው ቀሪውን ክፍያ እንዲፈጽሙ መደረጉንም በቅሬታቸው አካተዋል፡፡
ተጨማሪውን ክፍያ ካልፈጸማችሁ መታወቂያችሁ አያገለግልም መባላቸው አግባብነት እንደሌለውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡
የጤና መድኅን ተጠቃሚዎች አነስተኛ የገንዘብ አቅም እንዳላቸው አስታውሰው፤ ጭማሪው ያለባቸውን የኑሮ ጫና እንደሚያባብስ አስረድተዋል፡፡
የጤና መድኅን ተጠቃሚዎቹን ቅሬታ የያዘው አሐዱ የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ምክትል ስራ አስፈጻሚ ሽመልስ አረጋን ምላሽ ጠይቋል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው በምላሻቸው፤ በፌደራል ደረጃ የተቋቋመና በጠቅላይ ሚንስቴር የሚመራ ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ምክር ቤት መኖሩን ገልጸው፤ ጭማሪው የዚህ ምክር ቤት ውሳኔ መሆኑን ነግረውናል፡፡
የጭማሪው ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ የሚገኘው የመድኃኒቶች ዋጋ መናር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡ አዲሱ ጭማሪም የጤና መድኅንን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ የወሰነው ጭማሪ የማኅበረሰቡን የገቢ መጠን ያገናዘበ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በዚህኛው ዓመት ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዓመታዊው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የነባር አባላት እድሳት እና የአዲስ አባላት ምዝገባ ከተያዘው የጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ በአገር አቀፍ ደረጃ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በዓለምነው ሹሙ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ብሄራዊ ፓርኮች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ተባለ
👉በባቢሌ መጠለያ የዝሆኖችን ቁጥር ያመናመነው ችግር አሁንም አልተቀረፈም ተብሏል
ጥቅምት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሕገወጥ ሰፈራ፣ ሕገወጥ አደን እና ግጦሽ በብሄራዊ ፓርኮች ላይ አሁንም ፈተና ሆነዋል ሲል የኢትዮጲያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ27 በላይ ብሄራዊ ፓርኮች እንደሚገኙና 13 የሚሆኑት ብሄራዊ ፓርኮች በባስልጣን መስሪያ ቤቱ እንደሚስተዳደሩ የተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ናቸው፡፡
እነዚህ ብሄራዊ ፓርኮች በሕገ ወጥ ሰፈራ፣ በሕገወጥ አደን እና ግጦሽ በአጠቃላይ በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት አሁንም ጫና ውስጥ እንደሚገኙ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
አክለውም፤ ብሔራዊ ፓርኮች እና የዱር እንስሳት መጠለያዎች ላይ የሚስተዋሉ ሰው ሰራሽ ጫናዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመራቸው በተፈጥሮ ሀብቱ ላይ የህልውና ስጋት መደቀኑን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም በእነዚህ ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት በፓርኮቹ ውስጥ የሚገኙ እንዳንድ የእንስሳት ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ እንደተደቀነባቸው ተናግረዋል፡፡
ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ብሄራዊ ፓርኮችን ለሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ለስነ ምህዳራዊ ጠቀሜታዎችን እንዲሰጡ ለማስቻል፤ ለማሕበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤን የመፍጠር ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በኦሮምያ እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የሚገኘው “ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ” በሕገ-ወጥ አደን፣ ባልተጠና አሰፋፈር እና የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ምህዳር ባልጠበቀ ኢንቨስተመንት ጉዳት ሲደርስበት መቆየቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
ለዝሆኖች መጠለያነት በተከለለው ጥብቅ ቦታ የሚከናወነውን ሕገ-ወጥ ሰፈራ ለመከላከል እንዲሁም የሚነሱ ችግሮችን በዘለቄታ ለመፍታት ከኦሮምያ እና ሶማሌ ክልል ኃላፊዎች ጋር ለመወያየት እቅድ መያዙንም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ እንደ ችግር የሚነሱት ሕገ-ወጥ አደን፣ ሰፈራ እና ኢንቨስትመንት ያልተቀረፉት በትብብር መስራት ባለመቻሉ እና የግንዛቤ እጥረት በመኖሩ መሆኑን አቶ ሰለሞን አንስተዋል፡፡
የመጠለያው ችግር ከተቃለለ በመመናመን ላይ የሚገኘው የዝሆኖች ቁጥር የመጨመር እድል እንዳለውም አመላክተዋል፡፡
በአጠቃላይ በብሄራዊ ፓርኮች እና የዱር እንስሳት መጠለያዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የተለያዩ የሕግ ማስከበር ሥራዎችም እየተከናወኑ እንደሚገኙ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በኦሮሚያ ክልል በአራቱም የወለጋ ዞኖች ያለው የጤና መድህን ተጠቃሚ የአባላት ምዝገባ አሁንም ከ50 በታች መሆኑ ተገለጸ
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት በየአመቱ የሚታደሰው ከተያዘው ጥቅምት ወር ጀምሮ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ክልሎች እያደረጉት ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል ሲል አሐዱ የኦሮሚያ፣ የሃረሪ እና የጋምቤላ ክልሎችን አነጋግሯል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የሃብት ማሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ዲንቃ ኢረና የክልሉ ጤና ቢሮ ባለፈው ዓመት 28 ሚሊየን 8 መቶ ተጠቃሚዎችን መዝግቦ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን በወለጋ አራቱም ዞኖች ማለትም በቄለም፣ ሆሮ ጉድሩ፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ባለው የሰላም እና የጸጥታ ችግር ምክንያት ተጠቃሚዎች አናሳ መሆናቸውን ገልጸው፤ የአባላት ምዝገባ የሚያከናውኑ ሰራተኞችም ወደ አካባቢዎቹ ገብተው ለመመዝገብ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በአራቱም የወለጋ ዞኖች ያለው የጤና መድህን ተጠቃሚ የአባላት ምዝገባ አሁንም ከ50 በታች መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዘንድሮው ዓመት 29 ሚሊየን ተጠቃሚዎች እና 7 ቢሊየን ብር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አቶ ዲንቃ ተናግረዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ቾልቶት ቦል በበኩላቸው፤ ካሉት 14 የጤና መድህን ተጠቃሚ ወረዳዎች ውስጥ አሁን ላይ 12 የሚሆኑት አግልገሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም በተያዘው ዓመት ወደ አገልግሎት ያልገቡ እና በከፊል የጀመሩ ሁለት ወረዳዎችን በመጨመር ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየታሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሐረሪ ክልል አሁን ላይ በጤና መድህን አገልግሎት መቶ ከመቶ በማስመዝገብ ጥሩ ውጤት አለን ያሉት ደግሞ፤ በክልሉ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አስተባባሪ አቶ ጀማል መሐመድ ናቸው፡፡
አስተባባሪው አክለውም በዘንድሮው ዓመትም አዳዲስ ተመዝጋቢዎችን ለመቀበል እና 48 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ የአምና ገቢው 24 ሚሊየን እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ የሚገኙ ተጠቃሚዎች የማሳደሻ ገንዘብ ጭማሪ ተደርጎብናል የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውም አይዘነጋም፡፡
በእመቤት ሲሳይ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የምዕራባውያኑ እና የአሜሪካን ዝምታ በራሱ በምስራቅ አፍሪካ ያለዉን ዉጥረት ማባባስ ነዉ ሲሉ የፖለቲካ ምሁራን ገለጹ
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በባህር በር እንዲሁም በአባይ ጉዳይ ከግብፅ ጋር ዉጥረት ዉስጥ መግባቷ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በሁለቱ ሀገራት ጉዳይ ቱርክ ለማደራደር ጥረት ብታደርግም አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ግን ዝምታን መርጠዋል።
የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ በለጠ ሲሳይ ስለ ጉዳዩ ሲያብራሩ፤ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ምስራቅ አፍሪካ ላይ በተለይም የአባይ ተፋሰስ እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ አይን የሆነዉ እና ከፍተኛ የንግድ ግንኙነት የሚካሄድበትን የቀይ ባህር ጉዳይ የሚነካ እስካልሆነ፣ ያላቸዉን ፍላጎትና ጥቅም እስካልነካ እና እስካልተጋፋ ድረስ ጣልቃ የሚገቡበት ምክንያት እንደሌለ አንስተዋል፡፡
አክለውም፤ ̎ምዕራባዉያኑም ሆነ አሜሪካ ልክ በሌሎች የመካከለኛዉ ምስራቅ ሀገራት እንደሚያደርጉት በተዘዋዋሪም ቢሆን በእጅ አዙር በግብፅ በኩል የተለያዩ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ የጦር መሳሪያ ድጋፎችን በማድረግ ፍላጎታቸዉን እያስፈጸሙ ይገኛሉ̎ ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
አምባሳደር ጥሩነህ በበኩላቸው፤ ̎አሁን ካለዉ የአለም ፖለቲካ የትኩረት አቅጣጫ አንጻር የመካከለኛው ምስራቅ ወዝግብ እንዲሁም ከቻይና እና ታይዋን ፍጥጫ አንጻር የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ጉዳይ ላይ እምብዛም ትኩረት እየሰጡት አይደለም̎ ሲሉ አብራርተዋል።
አክለውም፤ ̎ጉዳዩ ሁለቱ ሀገራት የገቡበትን ዉጥረት በድርድር የማይፈቱ ቢሆን እንዲሁም ደም አፋሳሽ ጦርነት የመሳሰሉት ነገሮች ቢታከሉበት ኖሮ ምዕራባውያኑ ጉዳዩን በትኩረት ይከተላሉት ነበር̎ ብለዋል።
"አሁንም ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን በማዳከም ሥራ ላይ ተጠምደዋል" ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፤ በምስራቅ አፍሪካ ያለዉን ዉጥረትንም አስመልክቶ ምንም ማለት እንደማይፈቅዱ ገልጸዋል፡፡
ምሁራኑ አክለውም፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ጉዳይ ብሎም የምስራቅ አፍሪካ የገቡበት ዉዝግብ የምዕራብዉያንን ብሔራዊ ጥቅም እስካልነካ ድረስ ጣልቃ ይገባሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በፅዮን ይልማ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በመዲናዋ የአደባባይ አጥር ላይ በተሽከርካሪ ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ 196 ሺሕ ብር ተቀጣ
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የአደባባይ አጥር ላይ በተሽከርካሪ ጉዳት ያደረሰ ግለሰብን በገንዘብ መቅጣቱን አስታውቋል።
አ/ቶ ሱራፌል ተካልኝ የተባለ ግለሰብ ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 9:00 አካባቢ መኪና እያሽከረከረ ልዩ ቦታው ቴዎድሮስ አደባባይ ሲደርስ፤ የአደባባይ አጥር 07 ኮንክሪት ሙሌት አጥር ላይ ጉዳት ማድረሱን ባለስልጣኑ ገልጿል።
በዚህም የደረሰው የንብረት ጉዳት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ግምት መሠረት፤ ግለሰቡ 196 ሺሕ 809 ብር መቀጣቱ ተነግሯል።
በዚህም ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ ተጠያቂ በማድረግ በመመሪያው መሰረት የገንዘብ ቅጣቱ ለክፍለ ከተማው ወረዳ 01 ፋይናንስ ጽ/ቤት ገቢ መደረጉ ተገልጿል።
ግለሰቡ የገንዘብ ቅጣቱን የተቀጣው የዲዛይንና ግንባታ ቢሮው በሚጠቀምበት የ2016 4ኛው ሩብ ዓመት የግንባታና ቁስ ዋጋ በመነሳት የዋጋው ግምቱ 196 ሺሕ 809 ብር በመሆኑ ነውም ተብሏል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው እለት የተለያዩ ሹመቶች መስጠታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።
በዚሁ መሠረት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመዋል፡፡
በተጨማሪም ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የቱርዝም ሚንስቴር ሚንስትር እንዲሁም፤ ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ የፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር በመሆን መሾማቸው ተገልጿል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ባለፉት ሁለት ወራት 13 የመገናኛ ብዙኃን ወደ ስርጭት መግባታቸው ተገለጸ
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ እስካለፈው ሰኔ 2016 ዓ.ም. ድረስ ፈቃድ ወስደው ስርጭት የጀመሩት 272 መገናኛ ብዙኃን ቁጥር ወደ 285 ከፍ ማለቱን የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ከዚህ በፊት በ2017 በጀት ዓመት 41 የመገናኛ ብዙኃን ወደ ስርጭት እንደሚገቡ፤ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቆ ነበር።
ታዲያ አሁን ላይ ስንት አዳዲስ የመገናኝ ብዙኃን ስርጭት ጀምረዋል? ሲል አሐዱ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን ጠይቋል።
በባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ ምዝገባ እና ዕውቅና ዴስክ ኃላፊ አቶ ደሴ ከፈለ፤ በተያዘው የ2017 ዓ.ም ሁለት ወራት ከ41ዱ የመገናኛ ብዙኃን ውስጥ 13 የግል የመገናኛ ብዙኃን ወደ ስርጭት መግባታቸውን ነግረውናል፡፡
በተጨማሪም 13 ሌሎች አዲስ የመገናኛ ብዙኃን ፍቃድ ወስደው ስርጭት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፈቃድ የወሰዱ የመገናኛ ብዙኃን ቅድመ ዝግጅታቸውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቀው ወደ ስርጭት መግባት እንደሚጠበቅባቸውም ኃላፊው አሳስበዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ዋጋ ልዩነት ላይ ያሳለፈው መመርያ በነጻ ገበያው ላይ ጣልቃ እየገባ ነው ማለት እንዳልሆነ ተገለጸ
ጥቅምት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ዋጋ መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነት መወሰኑ፤ በነጻ ገበያው ላይ ጣልቃ መግባት እንዳልሆነ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥቅምት 5 ቀን 2017 በውጭ ምንዛሪ መሸጫ እና መግዣ ዋጋ መካከል የሚኖረው ልዩነት ከ2 በመቶ እንዳይበልጥ መወሰኑ ተገቢ እንደሆነ ለአሐዱ ሐሳባቸውን የሰጡ የምጣኔ ሐብት ምሁራን አስታውቀዋል፡፡
̎የውጭ ምንዛሪውን ዋጋ ገበያው እንዲወስን የወሰነው መንግሥት የመሸጫ እና መግዣ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት የተጋነነ እንዳይሆን ብሔራዊ ባንክ ጣራ ማስቀመጡ ጣልቃ ገብነት አይደለም̎ ሲሉ ለአሐዱ የገለጹት የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪው ከፈለኝ ኃይሉ ናቸው።
ባንኮች የተከተሉት የውጭ ምንዛሪ አካሄድ ከመንግሥት እቅድ በተቃራኒው ሲሆን መሰንበቱን ገልጸው፤ በቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን በተለይ በወጪና ገቢ ሸቀጥ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
በዚህ የነሳተም የፋይናንስ ስርዓቱ እርምጃ በርካቶች በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የመንግሥት የቁጥጥር አቅም አስገምቶታል ብለዋል።
በተለይም የንግድ ባንኮች አካሄድ ብርቱ ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው የሌሎች አገራት ልምድ የጠቀሱት የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪው፤ የባንኮች ውድድር ለዶላር ዋጋ መናር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ነግረውናል ።
ብሔራዊ ባንክ የባንኮችን እንቅስቃሴ ሰርአት የማስያዝና የመከታተል ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ መመርያው ተገቢነት እንዳለው የሚናገሩት ደግሞ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሐብት ተመራማሪው ዶክተር አጥላው ዓለሙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሰርዓቱን ፈር ማስያዝ ከተሰጡት ሐላፊነቶች መካከል ግንባር ቀደሙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ̎ሐላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል̎ የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።
ዶክተር አጥላው፣ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመርያ መሰረት የማስተዳደርና ገበያውን እንደሚከታተል የተገለጸ በመሆኑ ለባንኮች ያሰራጨው ደብዳቤ ተገቢነት አለው ባይ ናቸው።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደራዊ እክሎች ዘርፉ በእጅጉ እንዲዳከም ፈር የቀደደ ከመሆኑም ባሻገር፤ የትችቶች ምንጭ ሲሆን መቆየቱን ዶክተር አጥላው አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ስርዓት ገበያ-መር እንዲሆን ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ፤ የውጭ ሀገር ገንዘቦች የምዛሪ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሻቅብ እና ገበያው እንዳይረጋጋ የባንኮች ሚና ከፍተኛ ሆኖ መቆየቱን ባለሙያዎቹ ከሰጡን ምላሽ ተረድተናል፡፡
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ
ጥቅምት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው በ13 መዝገብ የተከሰሱ ግለሰቦች ከአንድ ዓመት እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በ13 የክስ መዝገብ ተከሰው የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው፡-
1ኛ. ተካ ወ/ማርያም 25 ዓመት ጽኑ እስራት እና 28 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፤ በሌላ የክስ
መዝገብ ደግሞ 16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት፣
2ኛ. ለማ ተማሮ 10 ዓመት ጽኑ እስራት፣
3ኛ. መለሰ ካህሳይ 11 ዓመት ጽኑ እስራትና 76 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
4ኛ. ደመቀች ማጉጂ 15 ዓመት እስራት እና 30 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
5ኛ. ስምኦን ተወልደ 3 ዓመት ከ7 ወር እስራት እና 4 ሺሕ 500 ብር የገንዘብ ቅጣት ፣
6ኛ. ዮሃንስ ፍስሃዩ 5 ዓመት ከ7 ወር እስራትና 7 ሺሕ 500 ብር የገንዘብ ቅጣት፣
7ኛ. ሀና ዲኖ 3 ዓመት ከ3 ወር እስራትና 2 ሺሕ 500 ብር የገንዘብ ቅጣት፣
8ኛ. ረዳት ሳጅን መሀመድ አህመድ 6 ዓመት እና 8 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
9ኛ. ገ/ትንሳኤ ሀጎስ በ16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እና 80 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
10ኛ. አብዱል ሽኩር ይማም 10 ዓመት እና 11 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
11ኛ. ሙህዲን አማን መሀመድ 10 ዓመት እና 11 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
12ኛ. አብዱላዚዝ ራህመቶ ዳንቴቦ 5 ዓመት እና 6 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
13ኛ. ዘላለም ብርሃኑ 5 ዓመት እስራት እና 3 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
14ኛ. ናርዶስ ሀብቴ ደበሌ 4 ዓመት ከ5 ወር እስራት እና 3 ሺሕ 500 ብር የገንበዘብ ቅጣት፣
15ኛ. ፍሬሕይወት በላይ ግርማ 6 ዓመት እስራት እና 110 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት፣
16ኛ. ቅዱስ ኃ/ሚካኤል ሳምቢ 4 ዓመት ከ5 ወር እስራት እና 3500 ብር የገንዘብ ቅጣት፣
17ኛ. ሚኪያስ ተሾመ ፈጡላ 410 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት መቀጣታቸው ተነግሯል
በዚህም መሠረት፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በ13 የምርመራ መዝገቦች ሲታይ የቆየውን የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የወንጀል መዝገብ መርምሮ፤ ጥፋተኞችን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል በሚል ከአንድ ዓመት እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲሁም ከ2 ሺሕ ብር እስከ 410 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንደወሰነባቸው ተገልጿል።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ጊዜውን ያልጠበቀ ነው ሲሉ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ተናገሩ
ጥቅምት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስከረም 28 ማምሻውን ይፋ ያደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በግብርና ምርቶች ላይ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ሊያባብስ የሚችል እና ጊዜውን የጠበቀ ውሳኔ ነው ሲሉ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ከተለያዩ ስፍራዎች ተጓጉዞ ወደ መሀል አገርና ወደ ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚደርሰው የግብርና ምርት ዋጋ መጨመር የኑሮ ውድነቱ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር የቢዝነስ አማካሪው ከፈለኝ ኃይሉ ተናግረዋል።
̎የግብርና ምርት ዋጋ መጨመር የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሁለቱ ነገሮች የተያያዙ ናቸው̎ የሚሉት አማካሪው፤ መንግሥት የነዳጅን ድጎማ በሂደት አነሳለሁ እያለ ባለበት በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ የውጪ ምንዛሬ መጠን እየጨመረ መምጣቱን አንስተው፤ ̎የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ከሞኒተሪ ፖሊሲ በተጨማሪ የመንግሥት ወጪዎችን የመቀነስ ወይንም የፊሲካል ፖሊሲ ትግበራ ላይ በደንብ መታሰብ አለበት̎ ብለዋል፡፡
̎ውሳኔው ጊዜውን ያልጠበቀ አይደለም̎ የሚሉት ደግሞ የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዶክተር አጥላው ዓለሙ ናቸው።
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው አሁን ላይ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ያሉት ባለሙያው፤ ̎ይህም ዋና ዋና በሚባሉ አገልግሎቶችና ሸቀጦች ላይ የተጋነነ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል̎ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ተከትሎ የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ከ50 በመቶ እስከ መቶ በመቶ የሚደርስ ጭማሪ መደረጉን ያነሱት ባለሙያው፤ ይህም መሰረታዊ የአገልግሎት አሰጣጦች ላይ ጭማሪ እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡
̎የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር የትራንስፖርት ዋጋ ይጨምራል፤ የትራንስፖርት ዋጋ ሲጨምር ደግሞ የሚሰጡ አገልግሎቶችም የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪን መሰረት አድርገው ስለሚሰጡ መጨመራቸው አይቀርም̎ ያሉት ዶክተር አጥላው፤ ̎በአገሪቱ ውስጥ ምንም የኢኮኖሚ ችግር እንደሌለና የኑሮ ውድነት እንደሌለ ተደርጎ እየታየ ነው፡፡ ቢኖርም ደግሞ ምን አገባን የራሱ ጉዳይ የተባለ ይመስላል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጭማሪ እንዲደረግ የፈቀደው የነዳጅ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ ምክንያት መሆኑን የሚኒስትሩ አማካሪ አህመድ ሙሳ ነግረውናል።
አማካሪው አክለውም፣ ̎የግብርና ምርቶች ዋጋ መናር ከትራንስፖርት ወጪ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የሚታወቅ ቢሆንም መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ ጊዜውን የጠበቀ ነው̎ ብለዋል፡፡
በአማኑኤል ክንደያ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከፍልስጤማውያን ጎን እንደሚቆም አስታወቀ
ጥቅምት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከፍልስጤማውያን ጎን እንደሚቆም ፕሬዝዳንቱ ሲሪል ሪማፎሳ አስታውቀዋል፡፡
̎በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እንጠይቃለን̎ ያሉት ፕሬዝዳንት ሲሪል ሪማፎሳ፤ የታጋቾችን መፈታት እና የሰብአዊ እርዳታ ወደ ህዝቡ መድረስ እንዲረጋገጥ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት አዲሱን የስልጣን ዘመናቸውን የተረከቡበትን 100ኛ ቀን በማስመልከት በጆሃንስበርግ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር ነው፡፡
ራማፎሳ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት መንግስታቸው በተለይም በጋዛ ላይ እያደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመቃወም ለፍልስጤም ህዝብ ድጋፍ ለመስጠት ሙሉ ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዘዳንቱ መንግሥታቸው ለፍልስጤም ህዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ራማፎሳ በእስራኤል አቅራቢያ ባሉ እንደ ሊባኖስ ባሉ ሀገራት ላይ እያደረሰች የምትገኘው የቦንብ ጥቃት ያሳስበናል ሲሉም መደመጣቸውን አናዶሉ ዘግቧል።
በተያያዘ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች በፍልስጥኤማውያን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ያለምንም ውጤት እየተሳተፉ መሆናቸውን ግራ ዘመሙ የኢኮኖሚ ነፃነት አውጪ ፓርቲ (ኢ.ኤፍ.ኤፍ) አስታውቋል፡፡
የ22 አመቱ ደቡብ አፍሪካዊው አሮን ባይሀክ አልጀዚራ ባስተላለፈው ዘጋቢ ፊልም "The Ghost Unit" ላይ፤ በእስራኤል ኦፕሬሽን ሃይሎች (አይ.ኦ.ኤፍ) ውስጥ ተኳሽ እንደነበረ መለየቱን ገልጿል፡፡
ፓርቲው ̎ጉዳዩ ወደ ብሔራዊ አቃቤ ህግ (ኤን.ፒ.ኤ) እና መከላከያ መምሪያ ቀርቦና ተጣርቶ አስፈላጊ ከሆነ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ያደርጋል።̎ ያለ ሲሆን፤ ̎ማንኛውም አይ.ኦ.ኤፍን የሚቀላቀል ሰው ህጉን እየጣሰ ነው እናም መከሰስ አለበት።̎ ሲል አሳስቧል፡፡
ካለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ጀምሮ ጋዛን እየደበደበች የምትገኘውን እስራኤል በመቃወም ደቡብ አፍሪካ በ2023 መጨረሻ ላይ በሄግ በሚገኘው ፍርድ ቤት ክስ የመሰረተች ሲሆን፤ ቱርኪ፣ ኒካራጓ፣ ፍልስጤም፣ ስፔን፣ ሜክሲኮ፣ ሊቢያ እና ኮሎምቢያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በጥር ወር የህዝብ ችሎት የጀመረውን ክስ ተቀላቅለዋል።
እስራዔል በፍልስጤም እያደረሰች በምትገኘው ጥቃት በበዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ብዙዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። በተጨማሪም ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡
በታሪኩ አለሙ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#አሐዱ_ዓለምን_በሳምንት!
ጥንቅሩን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/JFSKRMhlXcg?si=k9M1h_hAhTshjFVF
#አሐዱ_ትንታኔ!
ትንታኔውን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/DOMCTTacvMk?si=_sMJmx5UCTnKqUZE
የሳይበር ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠሩ ሱዳናውያን ወንድማማቾች ክስ ተመሠረተባቸው
ጥቅምት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ)ሱዳናውያኑ ወንድማማቾች የተከሰሱት አገልግሎት ከማስተጓጎል ጀምሮ እስከ 10 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ኪሳራ በማድረስ ነው።
በቁጥር ሁለት መሆናቸው የተነገረው የ22 እና የ27 ዓመት ወንድማማቾች፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሳኝ በሆኑ መሠረተ ልማቶች እና በመንግሥት ኤጀንሲዎች ላይ በ10 ሺሕ የሚቆጠር የሳይበር ጥቃት በመፈፀም፣ የመረጃ ጠለፋ ቡድንን በመምራት እና መሰል ጥፋቶች መከሰሳቸውን የአሜሪካ የፍትሕ ዲፓርትመንት አስታውቋል።
ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል የዩናይትድ ስቴትስ ፍትሕ ዲፓርትመንት፣ የመከላከያ የስቴት ዲፓርትመንት፣ ኤፍ.ቢ.አይ፣ ማይክሮሶፍት እና ሪዮት ጌምስ እንደሚገኘበት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የቢራ ገብስ እና ጨውን ጨምሮ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች በዘመናዊ ግብይት ሊገበያዩ ነው
ጥቅምት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኢንዱስትሪ ምርት ናቸው ያላቸውን፤ የቢራ ገብስ፣ ጨው እንዲሁም የቆዳና ሌጦ ምርቶችን ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርዓት ለማስገባት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
"ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሶሶ ነው" ያሉት የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ፤ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ወደ ዘመናዊ ግብይት ለማስገባት ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የቢራ ገብስን እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ኢትዮጵያ ከውጭ ገበያ የምታስመጣው መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ "ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በተደረገው ጥረት ወደ ዘመናዊ ግብይት እንዲመጣ ተድርጓል" ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ አኩሪ አተር እዚሁ ሀገር ውስጥ ተዘጋጅቶና እሴት ተጨምሮበት ወደ ውጪ ሀገር የመላክ ሥራ እየተሰራ እንደሚኝም ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ ብሎም በዓለም ከፍተኛ የሚባል ሀብት ያላት ቢሆንም፤ ሀብቷን በሚገባ እየተጠቀመችበት አይደለም" ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የቆዳ ሀብቷን በአግባበቡ እንዳትጠቀም ማነቆ የሆነው ደግሞ የግብይት ስርዓቱ መሆኑን አብራርተዋል።
ስለሆነም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲሁም በተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጥናት ተደርጎ ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርዓት እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በኢንዱስትሪ ምርትነት የሚቀርበውን ጨውም፤ ወደ ዘመናዊ ግብይት ለማስገባት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የምርት ገበያ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን፤ ማዕድኖችን በተለይም የከበሩ ድንጋዮችን ሳፋየር፣ ኦፓል እና ኤመራልድ የተባሉትን ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርዓት ለማስገባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
#የአሐዱ_ዕለታዊ_ዜናዎች!
ዜናዎቹን ለመከታተል ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጠቀሙ👇
https://youtu.be/fFWm1Z7P80E?si=EAJbJr4RmZlAsTC3
"የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዶላር እጥረት የሚፈጠሩ የግብዓት እጥረቶችን ይቀርፍልኛል" ጤና ሚኒስቴር
👉የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት እና አጠቃቀም ከ8 መቶ ወደ 36 በመቶ ከፍ ብሏል
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርቡ የተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በዶላር እጥረት የሚከሰቱ የመድሃኒት ግብዓት እጥረቶችን ለመቅረፍ ያግዛል ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል፡፡
ማሻሻያው መድሃኒት አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ ከሀገር ውስጥ ባለፈም ለጎረቤት ሀገራት ምርቶችን ማቅረብ የምንችልበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
በዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዶላር እጥረት የሚጋጥሙ የግብዓት እጥረቶችን ለመቅረፍ በርካታ ዕድሎችን ይዞ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡
በሚሰሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች በበርካታ ሀገራት ያሉ ባለሃብቶች መዋለ ንዋያቸውን ጥያቄዎችን እያቀረቡና እጠየቁ መሆኑን ያነሱት ሚኒስቴሯ፤ ይህ ደግሞ ለህብረተሰቡ ግብዓት እንዳይቋረጥ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም ታች ድረስ ያለውን ተጠቃሚ ለማግኘት እና በእኩልነትና በፍትሃዊነት ለተጠቃሚ ማድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
̎በተለይም መድሃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶች ከመጡበት አንስቶ ህብረተሰቡ ጋር እስከሚደርስበት ድረስ በዋጋም ሆነ በተለያዩ ነገሮች ምንም ዓይነት ተጨማሪ ጫና እንዳይመጣ ሁሉም ተባብሮ ሊሰራ ይገባል̎ ብለዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለጤና ዘርፉ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የሚያነሱት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ፤ ̎በተለይም እንደ አፍሪካ 90 በመቶ የመድሃኒት ቅርቦት ከውጭ ሀገራት የነበረ በመሆኑ ይህንን የሚቀርፍ ነው̎ ብለውታል፡፡
አክለውም፤ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት እና አጠቃቀሟን ከ8 በመቶ አሁን ላይ ወደ 36 በመቶ ከፍ ማድረጓን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የመድሃኒት አቅርቦት ላይ ድጎማ የሚያደርግ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ሙዝ ጭኖ ሲመለስ የነበረ ጀልባ ጫሞ ሐይቅ ውስጥ ሰምጦ ከተሳፈሩ 16 ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ሲገኙ ሌሎቹን የመፈለግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከኮሬ ዞን አቡሎ አርፋጮ ከሚባል አካባቢ ሙዝ ጭኖ ሲመለስ የነበረ ጀልባ ጫሞ ሐይቅ ሰምጦ ከተሳፈሩ 16 ሰዎች ውስጥ ሁለቱ መገኘታቸውን የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ ገለጸ፡፡
የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ የሕዝብ ግንኙት እና ገጽታ ግንባታ ድቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ረታ ተክሉ እንደገለጹት፤ ትላንት ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የጀልባውን አሽከሪካሪ እና 15 የቀን ሠራተኞችን ከሙዝ ጋር ጭኖ ከኮሬ ዞን አቡሎ አርፋጮ ወደ አርባምንጭ ሲጓዝ የነበረ ጀልባው መስጠሙን ተናግረዋል ።
በጀልባው ላይ ከነበሩ 16 ሰዎች ሁለቱ በጀርካን ላይ ተንሳፈው የተረፉ ሲሆን፤ 14ቱ ባለመገኘታቸው ፖሊስ በፍለጋ ላይ መሆኑን ኮማንደር ረታ ተናግረዋል።
15 ተሳፋሪዎች በሙሉ ሙዝ ለመጫን ከአርባምንጭ ዙሪያ አካባቢ የሄዱ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመላቱ የጋሞ ዞን ኮሙኒኬሽን አስታውቋል ።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ከ44 ሺሕ በላይ ዜጎችን አቤቱታ መቀበሉን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ
👉 የግል ተቋማት የጠበቀውን ያህል አቤቱታ አላቀረቡም ተብሏል
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በ2016 ዓ.ም. ብቻ፤ የ44 ሺሕ 9 መቶ 12 ዜጎችን አቤቱታ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በ1 ሺሕ 9 መቶ 72 መዝገቦች የተቀበላቸው አቤቱታዎች፤ አስተዳደራዊ በደሎችን የሚመለከቱ ቅሬታዎች መሆናቸውን ገልጿል።
የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ተወካይ ደነቀ ሻንቆ፤ ግለሰቦች በአንድ መዝገብ ከአንድ በላይ አቤቱታዎችን ለተቋሙ ማቅረብ እንደሚችሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ2015 ዓ.ም. የተላለፉ እንዲሁም በ2016 ከቀረቡ አቤቱታዎች ውስጥ በአንድ ሺሕ 81 መዝገቦች ምርመራ እንደተካሄደባቸው ገልጸው፤ ከእነዚህ መካከል 81 በመቶ ወይም 8 መቶ 75 ያህሉ እልባት ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ ከቀረቡለት አቤቱታዎች መካከል የምርመራ ሂደታቸው ባለመጠናቀቁ ምክንያት እልባት ያልተሰጣቸው 83 መዝገቦች በክትትል ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
ቅድሚያ እና ልዩ ትኩረት ለሚሹ ዜጎች አፋጣኝ ምርመራ እንዲከናወን እንደሚደረግ የተገለጹት ተወካዩ፤ ከ93 በመቶ በላይ የሚሆኑት አቤቱታ አቅራቢ ዜጎች ቅሬታቸውን በአካል ተገኝተው ያቀረቡ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ተወካዩ አክለውም፤ ተቋሙ ባለፈው የበጀት ዓመት የግል ተቋማት ሠራተኞች የሚደርሱባቸውን አስተዳደራዊ በደል የተመለከቱ አቤቱታዎችን መቀበል መጀመሩን ገልጸው፤ "ነገር ግን ከተቋማቱ እየቀረቡ የሚገኙት አቤቱታዎች የተጠበቀውን ያህል አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የግል ተቋማት ሠራተኞች ቅሬታ የሚያቀርቡበትን አሰራር የዘረጋው፤ በተቋማቱ የሚያገለግሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎች እልባት የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ቢሆንም፤ እስካሁን የቀረቡ ቅሬታዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።
በግል ከፍተኛ ተቋማት ላይ የሚነሱ አስተዳደራዊ አቤቱታዎችን ለህዝብ እንባ ጠባቂ ማሰማት የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ፤ በተቋሙ 8 ቅርንጫፎች መገልገል እንደሚችልም አቶ ደነቀ ጨምረው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም "ዜጎች በከፍተኛ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ በደሎች የሚደርሱባቸው ከሆነ፤ የሰነድ ማስረጃዎችን በመያዝ በኦንላይን እንዲሁም በአካል አቤቱታቸውን ማቅረብ ይችላሉ" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
እምቦጭ በአዳዲስ ቦታዎች ላይ ስርጭቱ እየጨመረ እንደሚገኝ ተነገረ
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከዚህ ቀደም የእንቦጭ አረም ባልነበረባቸው የጣና ሀይቅ አዳዲስ አከባቢዎች ስርጭቱ እየተስፋፋ እንደሆነ ለአሐዱ የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከሁለት ዓመታት ወዲህ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ ሲካሄድ የነበረው እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስርጭቱ እየተስፋፋ እንደሚገኝ የጣና ሀይቅ የአካባቢ ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ የመጤ እና ተስፋፊ ዝርያ ክትትል እና ቁጥር ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኜ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት በደቡባዊ የጣና ሀይቅ ክፍል እና በጣቁሳ ወረዳ በአንድ ቀበሌ ብቻ የነበረው የእንቦጭ አረም፤ አሁን ላይ በ3 ወረዳዎች ላይ መከሰቱን አመላክተዋል፡፡
በአሁን ሰዓት ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ የጣና ሀይቅ ገባር ወንዞች ሞልተዋል፡፡ ይህም የአረሙ ስርጭት እንዲጨምር የተመቻቸ ሁኔታ ስለመፍጠሩ ነው የገለጹት፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ እምቦጭ አረም ዳግም በብዙሃን ሕይወት ላይ እንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የደቀነው ሥጋት ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን አንስተው፤ ባለፉት ዓመታት አረሙን በሰው ኃይልም ሆነ በማሽን በመታገዝ ለማስወገድ ጥረት ሲደረግ ቢቆይም በአረሙ አደገኛ የመራባት ባህሪ የተነሳ ዳግመኛ ስርጭቱን ማስፋቱን አስረድተዋል፡፡
ያለፈው ዓመት መረጃ ከ3 ሺሕ ሄክታር በላይ የሐይቅ ዳርቻ መሬት በእምቦጭ አረም መሸፈኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የአረሙ ስርጭት ምን ያህል ሄክታር መሬት እንደሸፈነ ግን በአሃዛዊ መረጃ አልተገለጸም፡፡
በ2016 ዓ.ም. የነበረው የዝናብ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ የነበረው የእንቦጭ አረም ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እንዳልነበር ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ እንደ አዲስ የተከሰተው የእንቦጭ አረም በምን ያህል ሄክታር እንደተሸፈነ ለማወቅ በሂደት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጨምረው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
"ከተፈቀደላቸው ግዜ በላይ ሐገር ውስጥ የሚቆዩ የውጭ ሀገር ዜጎችን እየቀጣሁ ነው" የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
ጥቅምት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው አስቀድሞ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ የተራዘመ ቆይታን በሚያደርጉ የውጭ ሐገር ዜጎች ላይ፤ ቅጣት እየጣለ እንደሚገኝ የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በተጨማሪም ሐሰተኛ ማስረጃ ይዘው የተገኙ የውጭ ዜጎች ላይ የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል፡፡
ከመጡበት ዓላማ ውጪ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የውጭ ሐገር ዜጎች መኖራቸውን የገለጹት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፤ አስቀድሞ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ እንዲያከናውኑት ከተፈቀደላቸው ተግባር ውጪ ሲንቀሳቀሱ በተያዙት ላይም እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ይህንን ሕግ በመተላለፍ ምን ያህል የውጭ ዜጎች እንደተቀጡ ባይጠቅሱም፤ "ከገንዘብ መቀጮ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ዳግም እንዳይመጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ይገኙበታል" ብለዋል፡፡
ተቋሙ የሚሰጣቸውን የቪዛ ዓይነቶች የደህንነት መቆጣጠሪያ እንዲካተትባቸው ያደረገው መሰል ተግባራትን ለመከላከል እንዲያስችለው ስለመሆኑ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ "በተሻሻለው የኢሚግሬሽን ማሻሻያ ከበድ ያሉ ቅጣቶች እንዲካተቱበት ተደርጓል" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ እና ከበርካታ ሀገራት ጋር ድንበር የምትጋራ እንደመሆኗ፤ ድምበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ሕገ-ወጥነትን ለማስቀረት የሚያግዙ በርከት ያሉ ጥናቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ እንደተካሄዱ እንደሚገኙም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
የኢሚግዜሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢትዮጵያ በርከት ያሉ ኮንፈረንሶች እየተከናወኑ በመሆኑ፤ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን የማስተናገድ አቅም የማሳደግ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥም በአየር እና በየብስ ኬላዎች ከ1 ሺሕ 141 በላይ መንገደኞችን ማገልገሉን አሳውቋል፡፡
የቱሪስት እና የቢዝነስ ተጓዦችን በስፋት ለማስተናገድም ለ188 ሀገራት ፈጣን የጉብኝት ቪዛ ተከፍቶ እንየሰራበት እንደሚገኝ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎች ምዝገባ በማቆማቸው መቸገራቸውን ተናገሩ
ጥቅምት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል በሁለተኛ ዙር የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲዎች የምዝገባ ጊዜ በመጠናቀቁ መቸገራቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ በሚገኘው ሃዲስ ዓለማየሁ የአዳሪ ትምህርት ቤት ከ600 የወሰዱትን ፈተና 560 እና 570 ያመጡ ተማሪዎች፤ የመረጡት ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል እንዳይችሉ "የመመዝገቢያ ግዜ ማለፉ እንቅፋት ሆኖብናል" ብለዋል፡፡
ሀምሌ 29 ቀን 2016 የተሰጠውን የመጀመሪያ ዙር ፈተና በጸጥታ ችግር ምክንያት መውሰድ ያልቻሉት ተማሪዎቹ፤ በሁለተኛ ዙር መስከረም 22 ቀን 2017 ፈተናቸውን ወስደው በሳምንቱ በተነገራቸው ውጤት ከፍተኛ ነጥብ ቢያስመዘግቡም፤ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጳውሎስ ሆስፒታል ያሉ የትምህርት ተቋማት 2ኛ ዙር ተፈታኞችን ባላገናዘበ መልኩ አዲስ ለሚቀበሏቸው ተማሪዎች የመግቢያ ፈተና ሰጥተው አጠናቀዋል፡፡
ለአሐዱ ሃሳሳቸውን ከሰጡ ተማሪዎች መካከል አንዷ በማህበራዊ ሳይንስ 560 በማጣት በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ብታስመዘግብም፤ ውጤቷን ከመስማቷ በፊት ልትማርባቸው የምትፈልጋቸው ተቋማት ምስገባ ማጠናቀቃቸው እንዳሳዘናት ትናገራለች፡፡
ውጤት ተጠናቆ ከመለቀቁ በፊት እንደ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ጳውሎስ የመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎች ምዝገባ ማጠናቀቃቸው ከፍተኛ የማለፊያ ነጥብ ያላቸው ተማሪዎች በመረጡት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ ማድረጉን ነግረውናል፡፡
ሌላው ከተፈጥሮ ሳይንስ 570 በማምጣት በሐገር አቀፍ ደረጃ 3ኛ የሆነው የሐዲስ ዓለማየሁ አዳሪ ት/ት ቤት ተማሪ ከአሃዱ ጋር በነበረው ቆይታ በዩኒቨርሲቲዎቹ የመማር ዕድል ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ሊሰካለት እንዳልቻለ ለአሐዱ ተናግሯል፡፡
በአማራ ክልል ባለው ፀጥታ ምክንያት በሁለተኛ ዙር ከተፈተኑት መካከል በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ብቻ 380 ተማሪዎች የተፈቱኑ ሲሆን፤ በተፈተኑ በሳምንታቸው ውጤታቸው ይፋ ተደርጎል፡፡
ተማሪዎቹም በከፍተኛ ነጥብ በማጠናቀቃቸውና በሀገሪቱ ባሉ ከፍተኛ ደረጃ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የሚመለከተው ማንኛውም አካል እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡
አሐዱም የተማሪዎቹን ጉዳይ ላይ የተማሩበት ትምህርት ቤት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር አቶ ደረጄ ከፈለኝ ጠይቋል፡፡
ሁኔታው ትምህርት ቤቱንም ሆነ ተማሪዎችን እንዳሳዘነ ያነሱት ርዕሰመምህሩ፤ "በአምስት ወራት ውስጥ ይህንን ያህል ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡ የሚያሻልም ድርጊት ነበር" ብለዋል፡፡
አዳሪ ትምህረት ቤቱ ካስፈተናቸው 33 ተማሪዎች ሃያ ሰባቱ ማለትም 82 በመቶ ከ500 በላይ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸው ትልቅ ድል መሆኑን አንስተው፤ የሚመለከተው አካል ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን በፍላጎታቸው መሰረት እንዲቀጥሉ እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጥ በአሐዱ የተጠየቀው ትምህርት ሚንስቴር "መረጃ የለኝም" የሚል አጭር መልስ ሰጥቷል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ለአራተኛ ጊዜ ዛሬ ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ በአዋሽ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት በአዲስ አበባ ተሰማ
ጥቅምት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት አከባቢ በአዋሽ ፈንታሌ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰምቷል፡፡
ትናንት ምሽት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት በመዲናዋ አሁንም ዳግም መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ ለኢቢሲ ሳይበር አረጋግጠዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ባለፈው በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ሲሆን፤ በአካባቢው ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴ አሁንም እንዳልቆመ ዶ/ር ኤሊያስ ተናግረዋል።
አሁን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት መጠኑ አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ኤሊያስ፤ በአዋሽ ፈንታሌ እና ሳቡሬ ከተማ መካከል ላይ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ እስከቀጠለ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ላይ በሬክተር ስኬል 4.9 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ በዚሁ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ መከሰቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በሳምንቱ እሁድ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም 4.6 ሆኖ የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ በአካባቢው ተከስቷል።
በተመሳሳይ ትናንት ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም ከምሽቱ 5፡11 ደቂቃ በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በአካባቢው የተከሰተ ሲሆን፤ የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱን ተናግሯል።
ይህ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በአስራ ሁለት ቀናት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ የተመዘገበ ነው።
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ በአብዛኛው አባል ሀገራት መፈረም የቀድሞዎቹን ስምምነቶች ከሥራ ውጪ ያደርጋል ተባለ
ጥቅምት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማእቀፍ ወደ ስራ እንዲገባ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ይህ ስምምነት እንዲፈረም እና ትግበራ ላይ እንዲውል ሀገራቱን ስትጎተጉት መቆየቷ ይታወቃል።
ባለፈው እሁድ የትብብር ስምምነቱ በ6 ሀገራት በመፈረሙ ምክንያት ወደ ሥራ እንደገባ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። አሐዱ የትብብሩ ወደ ሥራ መግባት ለኢትዮጵያ ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎችን ጠይቋል።
የቀድሞ ዲፕሎማት ዶክተር ተሻለ ሰብሮም ስምምነቱ ከአስሩ ሀገራት ስድስቱ መስማማታቸው ለኢትዮጵያም ይሁን ለፈራሚ ሀገራቱ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር ሱዳንን እና ግብፅን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሌሎቹን ሀገራት ግን ያገለለ እንደ ነበር አንስተው፤ ይሄኛው ስምምነት ግን ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ ቀጣናዊ ትብብርን ከማጠናከር ባለፈ፤ የውሃ ሃብት አስተዳደርን በተመለከተ ሚዛናዊ አካሄድ እንዲኖር እንደሚያደርግም ዶክተር ተሻለ አመልክተዋል፡፡
አንባሳደር ጥሩነህ ዜናው በበኩላቸው የትብብር ማእቀፉ መተግበር የተፋሰሱን የላይኛው ሀገራትን ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ግብፅ እና ሱዳን ከዚህ በፊት የነበራቸውን የበላይነት የሚያስቀር እንደሆነ ተናግረዋል።
የናይል ወንዝን በሚመለከት በተለይም በ1929 እና በ1959 የተፈረሙ የውሃ መጋራት ስምምነቶች ግብፅና ሱዳንን በእጅጉ የሚደግፉ እንደነበሩ የተናገሩት አንባሳደር ጥሩነህ፤ ይህ አዲስ የትብብር ማእቀፍ በአብዛኛው አባል ሀገራት መፈረሙ የቀድሞዎቹን ሱዳንን እና ግብፅን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምምነቶች ከሥራ ውጪ እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡
በተያያዘ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤ ፍትሐዊ እና እኩል ተጠቃሚነትን የሚያሰፍነውን የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ያልፈረሙ ሀገራት ስምምነቱን እንዲፈርሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ጥሪውን ያቀረቡት ከሲጂቲኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲሆን፤ በቃለ ምልልሱ ላይ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በተፋሰሱ አባል ሀገራት መካከል የልማት ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም ስምምነቱ ወደ ተግባር መግባቱ በናይል ወንዝ ተፋሰስ የውሃ ዲፕሎማሲ ጉዞ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ያልፈረሙ ሀገራት እንዲፈርሙ ጠይቀዋል፡፡
የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማእቀፍ ስምምነት ወደ ትግበራ መግባቱን ግብጽ እና ሱዳን እንደማይቀበሉት ማስታወቃቸው ይታወቃል።
በሚክያስ ኃይሌ
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
በአዲስ አበባ ለ3 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ተሰማ
ጥቅምት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ትናንት ምሽት ለሦስተኛ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ ሲሆን፤ የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱን ተናግሯል።
ትናንት ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም ከምሽቱ 5፡11 ደቂቃ ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በአስራ አንድ ቀናት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የተከሰተ ሲሆን፤ የመሬት መንቀጥቀጡ በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ መመዝገቡን አሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ድረገጽ አመላክቷል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ ከአዋሽ በሰሜን በኩል 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተከሰተ ሲሆን፤ ንዝረቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ተሰምቷል።
ከዚህ ቀደም መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ላይ በዚሁ አካባቢ በሬክተር ስኬል 4.9 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ በዚሁ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ መከሰቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በሳምንቱ እሁድ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም 4.6 ሆኖ የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ በአካባቢው መከሰቱ ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ትናንት ምሽት በኢትዮጵያ መሬት መንቀጥቀጥ ከማጋጠሙ በፊት፤ ቱርክ እና ኒውዝላንድን ጨምሮ በዘጠኝ ሀገራት ላይ ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ተዘግቧል፡፡
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ