🔹በሀገር ውስጥ ያሉ እና ጫት በሚጓጓዝበት መስመር ያሉ ሁሉም #ኬላዎች ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ ተወስኗል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ገብረመስቀል ጫላ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።
በዚህም መግለጫቸው ወደ ውጪ በሚላክ ጫት ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በዚሁ መሠረት በጫት ላኪነት የንግድ ፍቃድ ዘንድሮ ጭምር ያወጡት ዳግም ምዝገባ እንዲያከናውኑ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
በጫት ንግድ የተሰማሩ አዲስም ሆኑ ነባር ነጋዴዎች የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያዘጋጀውን መስፈርት ማሟላታቸው እየተረጋገጠና ግዴታ እየገቡ ፍቃድ ይወስዳሉ ብለዋል።
ለዳግም ምዝገባው የሚኖራቸው ጊዜ እስከ ህዳር 15 /2016 ድረስ እንደሚሆን አሳውቀዋል።
በተጨማሪ ሚኒስትሩ ፤ በሀገር ውስጥ ያሉ እና ጫት በሚጓጓዝበት መስመር ያሉ ሁሉም ኬላዎች ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ መወሰኑንም ይፋ አድርገዋል።
" ወደ ውጪ በሚላክ ጫት ላይ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራት እየበዙ መጥተዋል " ያሉት ሚኒስትሩ " በዚህም ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከሚላክ ጫት የምታገኘው ገቢ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ነው " ብለዋል።
ለአብነትም በ2015 ወደ ውጪ ከላከችው ጫት የተገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ከ144 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
ኮንትሮባንድን ጨምሮ የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት ለዚህ ምክንያት መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይህንኑ ለማስተካከል ሲባል ሁሉም ጫት ላኪ ነጋዴዎች በሚቀጥሉት 15 ቀናት ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ ተወስኗል ብለዋል።
አንዳንዶቹ ነጋዴዎች ፍቃዳቸውን ለሌላ ወገን በማስተላለፍ ያልተገባ ጥቅም እያገኙ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በ2013 ከጫት ወጪ ንግድ 402 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ፣ በ2014 ዓ/ም 392 ነጥብ 2ሚሊዮን ዶላር ፣ በ2015 ዓ/ም ደግሞ 248 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ማግኘቷ ተነግሯል።
መረጃው የሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ነው።
📢 አስደሳች ዜና! የኢሰመኮ የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልሞች ውድድር የኪነጥበብ ሥራ ማስገቢያ የመጨረሻ ቀን ተራዘመ!
🎉 በኪነጥበብ ሥራዎ ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የበኩልዎን አስተዋፅዖ ለማበርከት የሚያስችልዎት አጋጣሚ እንዳያመልጥዎ።
📅 አዲሱ የመወዳደሪያ ኪነጥበብ ሥራዎችን ማስገቢያ የመጨረሻ ቀን:- ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም.
📷 📽 ሰብአዊ መብቶችን የሚያሰርጹ ምናብ ከሳች ምስሎችን በካሜራዎ ሌንስ ያስቀሩ ወይም ቀልብ ሳቢ ታሪኮችን በአጭር ፊልም ይተርኩ። የኪነጥበብ ሥራዎን በፊልም ፌስቲቫላችን ላይ የማቅረብ፤ ተሽላሚም የመሆን ዕድልዎን አሁን ይጠቀሙ። ይፍጠኑ!
🔗 ስለውድድሩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ድረገጻችንን https://bit.ly/46sReAw ይጎብኙ።
" ለትግራይ ህዝብ ደህንነት የሚያሰጋ ነገር ከሌለ #ከመከላከያ_ሃይል ውጪ ያሉት የታጠቁ ሃይሎች ከትግራይ መሬት ከወጡ ትጥቅ ተሸክመን የምንኖርበት ምክንያት የለም " - አቶ ጌታቸው ረዳ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕረዚደንት ጌታቸው ረዳ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አንደኛ አመት በማስመልከት ከ " ትግራይ ቴሌቪዥን " ጋር ሰፊ ቃለመጠይቅ አድረገዋል።
በዚህም ቃለመጠይቃቸው ፥ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የትግራይ ግዛትን የተቆጣጠሩት ኃይሎችን ማስወጣትና ፣ በትግራይ ግዛት በአማራ ሃይሎች የተመሰረቱት አስተዳደሮች የማፍረስ ጉዳይ የፌደራል መንግስት ግዴታዎች ናቸው ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ፤ " የፕሪቶሪያ ውል የቶክስ ድምፅ የማቆም ስምምነት ነው " ያሉ ሲሆን ከዚህ አኳያ ስኬታማ ውልና ስምምነት ነው ብለውታል።
በቃለመጠይቁ ላይ ' ስለመሬት ይገባኛል ' ጉዳይም አንስተው የተናገሩት አቶ ጌታቸው " በአማራ ክልል በኩል ሃቅ የሚመስል የመሬት ይገባኛል ጥያቄ እንዳለ አስመስሎ የሚቀርብ አለ። በኔ አረዳድ እንደዛ አይነት ጥያቄ የለም ነው የምለው " ሲሉ ተደምጠዋል።
በኢትዮጵያ #የፌዴራል_መንግስት_ተደራዳሪዎች በኩል የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር አጨቃቂዎቹን የምእራብ ፣ ሰሜን ምእራብን ደቡብ ትግራይ ማስተዳደር የለበትም የሚሉ እንደነበሩ የክልሉ አስተዳዳሪ አንስተዋል።
አቶ ጌታቸው " ለትግራይ ህዝብ ደህንነት የሚያሰጋ ነገር ከሌለ #ከመከላከያ_ሃይል ውጪ ያሉት የታጠቁ ሃይሎች ከትግራይ መሬት ከወጡ ትጥቅ ተሸክመን የምንኖርበት ምክንያት የለም " ያሉ ሲሆን " የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የፈረምነው የትግራይ መሬት ቆርሰን ለመስጠት ሳይሆን ፤ በህገ-መንግስት መሰረት ይፈታ ስለተባለ ነው " ብለዋል።
ከተፈናቃዮች መመለስ ጋር በተያያዘም የትግራይ ምእራባዊና ደቡባዊ አከባቢዎች እንዲሁም ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው የመመለስ ጉዳይ ቀደም ብሎ መፈፀም የነበረበት ተግባር እንደነበር ገልጸዋል።
" ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት ተፈናቃዮች እስከ ሰኔ 21/2015 ዓ.ም ወደ ቄያቸው ይመለሳሉ ብሎ የገባውን ቃል አልፈፀመም " ብለዋል።
የሰላም ስምምነት ትግበራው እንዲፋጠን ከአማራ ክልል አመራሮች ለመስራት ጥረት መደረጉን ያነሱት አቶ ጌታቸው " በፕሪቶሪያ ውል ላይ መደራደርና መገምገም ስለጀመሩ ዉይይቱ ተቋረጠ " ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ በቃለመጠይቁ የሪፈረንደም ጉዳይም ተነስቶ ነበር።
አቶ ጌታቸው ሪፈረንደም ለማካሄድ የትግራይ ክልል ተወካዮች ምክር ቤት የግድ መቋቋም እንዳለበት ተናግረዋል።
" ከዚህ ውጭ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ሪፈረንደም የማካሄድ ህገ-መንግስታዊ ስልጣን የለውም " ሲሉ አሳውቀዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ፤ " የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሪቶሪያ ውል እንዳይፈፀም እግር እየጎተተ ነው የሚለው ንግግር የተጋነነ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፤ #የአፍሪካ_ህብረት ግጭት ዳግም እንዳይነሳ በማረጋገጥና ውሉ በተማሏ መንገድ እንዲፈፀም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስገንዝበው " ሁሉም ልዩነቶች ሰላም ብቻ ነው መፈታት ያለባቸው ፣ ከጥይት ቶክስ #ለውይይት ቦታ መስጠት አለብን። ትግራይ የአውዳሚ ጦርነት መነሃሪያ እንድትሆን አንፈቅድም። " ብለዋል።
አቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳደራቸው ዋና ትኩረት የትግራይ ህዝብ #ደህንነት_ማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸው ፤ " የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀስ ማኛውም አካል ወይም ሃይል ተቀባይነት የለውም እንታገለዋለን። " ብለዋል።
በትላንትናው ዕለት የፌዴራል መንግሥት ባወጣው መግለጫ ፦
- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአንዳንድ ነገሮች ወደኋላ እየቀረና የሰላም ስምምነቱን በተሟላ ሁኔታ ሳይፈፅም እያነከሰ ነው ሲል መተቸቱ ፤
- አከራካሪ የሚባሉ አካባቢዎችን በተመለከተ አቋም ወስዶ እንደሰራ እንደሆነ ፤ ክረምት ደርሶ የእርሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ፣ የአካባቢ ነዋሪዎች በመረጧቸው አካላት እንዲተዳደሩ፣ በመጨረሻም ደረጃ በደረጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን እና ይሄንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ማስታወቁ ፤
- የሰላም ስምምነቱ #በተሟላ_ሁኔታ_እንዲፈፀም ማድረግ ያለበትን ሁሉ ቢደረግም በዚያኛው ወገን እግር የመጎተት አዝማሚያ እንደሚታይ መግለፁ አይዘነጋም።
#Amhara
በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሐፊ ዶ/ር አስማረ ደጀን፤ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎችን አቋም በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረው መረጃ " #የተሳሳተ ነው " አሉ።
ከሰሞኑን በአማራ ክልል ስላሉ ዩኒቨርሲቲዎች ምንድነው የተባለው ?
ከቀናት በፊት ቪኦኤ ሬድዮ ጣቢያ የፎረሙን ዋና ጸሐፊ የሆኑትን ዶ/ር አስማረ ደጀንን ዋቢ በማድረግ ባወጣውና ቲክቫህ ኢትዮጵያም ባጋራው ዘገባ ፤ በአማራ ክልል የሚገኙ የ10 ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች ከክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አኳያ የመማር ማስተማር ሂደትን ማስቀጠል ይቻል እንደሆነ ውይይት ካደረጉ በኃላ ሁኔታው #በቅርቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማስቀጠል የሚያስችል እንዳልሆነ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
በተጨማሪ ዶ/ር አስማረ ደጀን ለሬድዮ ጣቢያው በሰጡት ቃል፤
* ተማሪዎች ገብተው ግጭቶች በሚመጡበት ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊነት እንደማይወስዱ፤
* ዩኒቨርሲቲዎች ለ2016 የሚሆን የምግብ አቅርቦት ማዘጋጀት የነበረባቸው ቢሆንም አቅራቢዎቹ ከቦታ ቦታ ፤ ምርት ካለበት ቦታ ሄደው ተዘዋውረው መግዛት ስላልቻሉ የምግብ ግብአቶች በጠቅላላው ተማሪን ሊያስጠራ የሚችል እንዳልሆነ ገልፀዋል።
ፎረሙ ትምህርት ሚኒስቴር " ለ2016 ትምህርት በአሁን ሰዓት ተማሪዎችን ጥሩ እያለ ነው " ብሎ ለፀጥታው ኃላፊነት የሚወስድ አካል ከሌለ ይህን ማድረግ #እንደሚያስቸግር ነው የገለፀው።
ከዚህ ባለፈ የፎረሙ አባልና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ፤ በአካባቢው የቀጠለው አለመረጋጋት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ እንደማያስችል ከተስማሙት የፎረሙ አባላት እንደሆኑ ገልጸዋል።
ያለው ሁኔታ ካልተሻሻለ በስተቀር አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ግቢ ውስጥ ተማሪ ማስገባት በእጅጉ ፈታኝ እንደሚሆንና ለልጆችም ደህንነት በጣም አስጊ መሆኑን ፕሬዜዳንቱ ለጣቢያው ተናግረዋል።
ይህ መረጃ ከተሰራጨ ከቀናት በኃላ የፎረሙ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር አስማረ ደጀን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዛሬ በሰጡት ቃል " ሰሞኑን የተሰራጨው መረጃ በአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ያልተባለና ስህተት ነው " ብለዋል።
በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ለመቀበል አመች ሁኔታዎችን እየተጠባበቁ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን መጥራት መጀመራቸውንም ገልጸው፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ጥሪ ማስተላለፉን ለአብነት አንስተዋል፡፡
"አብዛኞቹ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እየጠሩ ነው" ያሉ ሲሆን " ብዙ ተማሪዎችን በአንድ ጊዜ ለመጥራት ግን የግብዓት ችግር ለተቋማቱ እንቅፋት ሆኗል " ብለዋል።
ዶ/ር አስማረ፤ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ግብዓት አቅራቢዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለማቅረብ የተቸገሩ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ መሆኑን አሳውቀዋል። በየአካባቢው ያሉ አቅራቢዎች ግብዓት እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን ተቀበሉ በሚልበት ጊዜ የማይቀበሉበት ምክንያት እንደሌለም ገልጸዋል።
" ክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር እየተሻሻለ ከመጣ ተቋማቱ ተማሪዎቻቸውን ወዲያው ይጠራሉ፤ ተማሪዎችን አይጠሩም የተባለው ስህተት ነው፤ አልተባለምም " ሲሉ ተናግረዋል።
አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ግብዓት ለማግኘት ከመቸገራቸው ውጭ የመማሪያ ክፍሎችን አጽድተዋል፣እድሳት የሚያስፈልጋቸውንም አድሰው ለትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ዝግጁ ሆነዋል ሲሉ ለክልሉ ሚዲያ ተናግረዋል።
#Update
የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አንደኛ ዓመት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
በዚህም መግለጫ የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲከበር ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል።
በአከራካሪ ቦታዎች ተፈናቃዮች እንዲመለሱና በህገመንግቱ መሰረት ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቋም ይዞ ተግባር ላይ እንዳለ አመልክቷል።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን መንግሥት በጦርነቱ የመጨረባ ወቅት ምንም እንኳን ሁሉን ነገር በኃይል ለመፈፀም የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና የነበረው ቢሆንም ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ቢቋጭ ሀገርን አትራፊ የሚያደርግ መሆኑ ስለታመነበት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም መደረጉን አስታውሷል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ውሳኔ " ሀገርን ለመገንባትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ሲባል የተከፈለ መሥዋዕትነት ነው " ብሎታል።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መንግሥት በሆደ ሰፊነትና ቁስሉ እንዲሽር ካለው ፍላጎት ረጅም ርቀት መጓዙን ገልጿል። ወደ ትግራይ በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ ልዑክ መላኩ ፤ በፍጥነት የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የባንክ ፣ የአውሮፕላን አገልግሎት መጀመሩን በማሳያነት አንስቷል።
በተጨማሪም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ ተደርጎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል ብሏል።
የኮሚኒኬሽን አገልግሎቱ በዚህ መግለጫው ፤ የፌዴራል መንግሥት አንዳንድ ነገሮችን እያገዘ ፤ አንዳንድ ነገሮችን ችሎ እያለፈ፣ አንዳንድ ነገሮችን እየመከረ አንዳንድ ነገሮችንም ራሱ እየሠራ የሰላም ስምምነቱ በተሟላ መልኩ በሂደት እንዲፈጸም ለማድረግ መሞከሩን አመልክቷል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአንዳንድ ነገሮች ወደኋላ እየቀረና ስምምነቱን በተሟላ ሁኔታ ሳይፈጽም እያነከሰ ለክልሉ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ የፌዴራል መንግሥቱ እንዳላቋረጠ በመግለጫው ተገልጿል።
መግለጫው የክልሉ ጊዜያዊ አስገዳደር በምን በምን ጉዳዮች ወደኃላ እንደቀረ በግልፅና በዝርዝር አልገለጸም።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ፤ አከራካሪ የሚባሉ አካባቢዎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ አቋም ወስዶ እንደሰራ እንደሆነም ይፋ አድርጓል።
" የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም ወገን በሚጠቅም መንገድ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ብልጽግና በሚያረጋግጥ መንገድ መፍትሔ መሰጠት አለበት " የሚል እንደሆነ አመላክቷል።
🔹ክረምት ደርሶ የእርሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ፤
🔹የአካባቢ ነዋሪዎች #በመረጧቸው አካላት እንዲተዳደሩ፤
🔹በመጨረሻም ደረጃ በደረጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት #ሕዝበ_ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡንና ይሄንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አሳውቋል።
" ይህ ሁሉ ቢደረግም እንኳን በዚያኛው ወገን እግር የመጎተት አዝማሚያ ይታያል፡፡ " ያለው መግለጫ " ይህ ግን ዘላቂ ሰላምን፣ ብልጽግናንና የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አያረጋግጥም ብሏል።
የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶርያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠበቅበት በላይ መጓዙን፤ በዚህም ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ደጋግሞ ማሳየቱን የኮሚኒኬሽን አገልግሎት አመልክቷል።
የፕሪቶርያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲከበር መንግሥት አሁንም ቁርጠኛ አቋም እንዳለው
ሁሉም አካላት ተመሳሳይ ቁርጠኝት በማሳየት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝቧል።
(ሙሉ መግለጫእ ከላይ ተያይዟል)
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት ለመማር አመልክታችሁ ተቀባይነት ላገኛችሁ የመግቢያ ፈተና የፊታችን እሁድ እንደሚሰጥ ኮሌጁ አሳውቋል።
የፈተና ቀን፦ ጥቅምት 25/2016 ዓ.ም ጠዋት 2:00
የፈተና ቦታ፦ መድኃኔአለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
ተፈታኞች መታወቂያ፣ እስኪብርቶ፣ እርሳስ፣ መቅረጫ እና ላጲስ መያዝ ይጠበቅባችኋል። መታወቂያ ያልያዘ ተፈታኝ ወደመፈተኛ ክፍል መግባት እንደማይችል ኮሌጁ አሳስቧል።
ለፈተናው የተመረጡ አመልካቾች ዝርዝር በኮሌጁ ድረገጽ ላይ ማግኘት የሚችሉ ሲሆን ቅሬታ ያላቸው አመልካቾች እስከ አርብ ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም ጠዋት 4:00 በኮሌጁ ሬጅስትራር በመገኘት ቅሬታቸውን ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
የድሬዳዋ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ጉዳይ መፍትሄ አግኝቷል ?
ዛሬ የድሬዳዋ መካነ ኢየሱስ ማህበረ ምዕመናንን ወቅታዊ ሁኔታ በመሚመለከት በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ መግለጫ ሰጥታለች።
በዚህም መግለጫ ፤ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፤ የድሬዳዋ ማህበረ ምዕመናን የቤተ ክርስቲያን ህንጻና ሌሎች ተያያዥ ህንጻዎች ያሉበትን ይዞታ ለሌላ አገልግሎት ለማዋል በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የተላለፈው ውሳኔ ቤተ ክርሰቲያኗን ብቻ ሳይሆን መላውን ህዝበ ምዕመን በእጅጉ ማስደንገጡ ተገልጿል።
ይህ ውሳኔ እንደገና እንዲጤን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር ብርቱ ክትትል በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ተመላክቷል።
የከተማው አስተዳደርም በተለይም ከንቲባው ሁኔታውን በጥንቃቄና በሃላፊነት ስሜት እየተከታተሉ ሲሆን ከቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ጋርም ለመምከር ቀጠሮ መያዛቸው በመግለጫው ላይ ተመላክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩ የማይመለከተውና በየትኛም መንገድ ድርሻ የሌለው አንድ አካል፤ ችግሩ መፍትሔ እንዳገኘ አድርጎ በዛሬው ዕለት በራሱ ማህበራዊ ገጽ (Facebook) የተሳሳተ መረጃ አውጥቷል ብሏል የቤተክርስቲያንኒቱ መግለጫ።
ስም ያልጠቀሰው መግለጫው ይኸው አካል ይህንን ስህተት በአስቸኳይ እንዲያርም ጥብቅ ማሳሰቢያ የደረሰው መሆኑን ገልጿል።
ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከምታውቀው ድረስ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ምንም ዓይነት ውሳኔ ያልተሠጠ መሆኑንና ለወደፊትም ቤተ ክርስቲያኒቱ በራስዋ አሠራር ኦፊሴላዊ መረጃ እስከምትሰጥ ድረስ ህዝበ ምዕመኑ በትዕግስትና በጸሎት እንዲጠባበቅ አሳስባለች።
#BongaUniversity
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የነባር መደበኛ፣ ማታ እና ሳምንት መጨረሻ መርሐግብር የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች ምዝገባ የሚካሔደው ጥቅምት 29 እና 30/2016 ዓ.ም መሆኑን አሳውቋል፡፡
ስለሆነም በተጠቀሱት ቀናት በዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራር በአካል በመገኘት እንድትመዘገቡ ተብሏል፡፡
#ለጥንቃቄ
ቴሌግራም ላይ ከተለያዩ ሰዎች አጭር ጹሑፍና ሊንክ እየተላከሎት ነው ?
ቴሌግራም ላይ ከተለያዩ ሰዎች ጹሑፍና ሊንክ ያለው መልዕክቶች እየተላኩ ነው። ብዙዎች ይህ ጉዳይ በተደጋጋሚ እየደረሳቸው እንደሆነና የጥንቃቄ መልዕክቱን እንድናስተላልፍ ጠይቀውናል።
በመልዕክት የሚላከው ሊንክ ምንድን ነው?
በመልዕክቱ አብሮ የሚደርሶት ሊንክ የቴሌግራም አካውንቶን ለመጥለፍ የተዘጋጀ ቴሌግራምን የሚመስል ድረ-ገጽ ነው። ሊንኩን ሲከፍቱት ስልክ ቁጥር አስገብተው ወደ ቴሌግራም እንዲገቡ ይጠይቆቃል።
ቁጥሮን አስገብተው የሚመጣው ሌላኛው ገጽ በቴሌግራሞት የተላከሎትን አጭር የማረጋገጫ ቁጥር እንዲያስገቡ የሚጠይቅ ነው።
የተላከሎትን የማረጋገጫ ቁጥር ካስገቡ የእርሶን ቴሌግራም በቀጥታ ይህን ወጥመድ ያዘጋጁ ሰዎችም መጠቀም ይጀምራሉ። በዚህም መልዕክቶችን ለሌሎች መላክና እርሶ እንደላኩት አድርገው ማቅረብ ይችላሉ።
ይህ ገጽ ልክ ቴሌግራምን እንዲመስል ተደርጎ የተሰራ ሲሆን የሚያስገቡት መረጃ ግን ወደ ቴሌግራም ሳይሆን ይህንን ወደ ሚቆጣጠሩት ሰዎች የሚላክ ነው። ይህ አይነቱ ማጭበርበር ማጥመድ (Phishing) በመባል ይታወቃል።
ምን ማድረግ እችላለሁ ?
ይህ ችግር ካጋጠሞት ቀጥታ ቴሌግራሞት ላይ Setting ላይ በመግባት #Device የሚለውን በመጫን የእርሶ አካውንት በምን በምን ስልኮች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ማየት ይችላሉ። በዚህም ከእርሶ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ስልኮችን በሙሉ ማስወጣትና እርሶ የሚጠቀሙበትን ብቻ ማስቀረት ይችላሉ።
ሁለተኛው መንገድ ይህ ችግር ከተመፈጠሩ በፊት የሚያገለግል ሲሆን ሁለተኛ ዙር የደኅንነት ማረጋገጫ (Two-Step verification ) መጠቀም ድንገት ለእንደዚህ አይነት ችግሮች ብንጋለጥ ተጨማሪ የደኅንነት ማረጋገጫ ይሆነናል። (ስለዚህ ዝርዝር ሊንኩን ተጭነው ያንብቡ)
#ትግራይ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት " ኃላፊነት የጎደለው ነው " በማለት እንደማይቀበለው አስታወቀ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፤ " የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተፈናቃዮች አስመልክቶ ባወጣው ሁለተኛው ዘገባ የፌደራል መንግስት ባደረገው ጥረት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ተጋሩ በብዛት ወደ ቄያቸው እንደተመለሱ፤ ሰብአዊ ድጋፍም እየቀረበላቸው እንደሆነ አስመስሎ ይፋዊ ዘገባ አውጥቷል " ሲል ገልጿል።
" በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጋሩ ከቄያቸው ተፈናቅለው በከፋ ሁኔታ በሚገኙበት ወቅት ፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ይመለሱ በማለት ሌተ ተቀን ቢወተውትም የወገኖቻችን መመለስ በሚመለከት አንዳች ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባልተደረገበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይህን መሰል ሃላፊነት የጎደለው ዘገባ ማውጣቱ ፤ ከአሁን በፊት በትግራይ ህዝብ ላይ ሲያደርስ የነበረውን በደል የሚያስቀጥል " ነው ብሏል።
ሪፖርቱ " በትግራይ ህዝብ ስቃይ መቀለድ ነው " ያለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር " ሆን ብሎ የዓለም ማህበረሰብ ለማሳሳት ያዘጋጀው ቅጥፈት ስለሆነ ተቀባይነት የለውም " ሲል ገልጿል።
የፌደራል መንግስት ይህን መሰል ሃላፊነት የጎደላቸው ዘገባዎች ሆነ ተብሎ በመዋቅሩ ሲለቀቁ የሰላም ሂደቱ የሚያውኩ ፣ መተማመን የሚያጎድሉ መሆናቸው ከግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢ እርምጃ ወስዶ እንዲያርም ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥሪ ማቅረቡን በመቐለ የሚገኘው የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከላይ ያለውን መግለጫ ካወጣው በኃላ አጭር መልዕክት በማህበራዊ ትስስር ገፁ አሰራጭቷል።
ኮሚሽኑ " በተፈናቃዮች 2ኛ ዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው የጂኦግራፊ ወሰኑ ትግራይን አልሸፈነም ይህም በዝግጅቱ ወቅት ተደራሽ ስላልነበረ መሆኑን እናረጋግጣለን " ብሏል። ኮሚሽኑ የተሳሳተ መረጃን ለማፅዳት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ (IRA) ጋር መተባበሩን እንደሚቀጥል አመልክቷል።
" ጥገናው አልቆ ኃይል ለመስጠት እስከ ሦስት ቀን ድረስ ሊወስድ ይችላል " - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ሙሉ በሙሉ በጭለማ እንዲዋጥ ያደረገ ስርቆት መፈፀሙ ተነገረ።
ከመንዲ አሶሳ በተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት ምክንያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሙሉ በሙሉ የኃይል አቅርቦት መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ጋይል አሳውቋል።
በክልሉ " መንደር 48 " በተለምዶ አንበሳ ጫካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶ አካላት ላይ በተፈፀመ ስርቆት መስመሩን የሚሸከሙ ሁለት የብረት ምሰሶዎች ወይም ታወሮች ወድቀዋል፡፡
በዚሁ የተነሳ ከመስመሩ ኃይል ሲያገኙ የነበሩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መዲና አሶሳ ከተማ እና የአሶሳ ዞን ወረዳዎች በሙሉ የኃይል አቅርቦት ተቋርጧል።
ከዚህ በፊትም በክልሉ ባምባሲ በተባለ አካባቢ በሥርቆት የተነሳ ኃይል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን አሁን ለኃይል መቋረጥ ምክንያት የሆነው አካባቢ ከአሶሳ ከተማ ወደ 30 ያህል ኪሎ ሜትሮች ርቀት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የወደቁ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በጊዜያዊነት በእንጨት ምሰሶዎች ለመተካት ጥረቶች የተጀመሩ ሲሆን ጥገናውን አጠናቆ ለአካባቢዎቹ ኃይል ለመስጠት እስከ ሦስት ቀን ድረስ ሊወስድ ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፤ የኤሌክትሪክ መሰረተልማቶችን መጠበቅ በየደረጃው ያሉ የሁሉም መስተዳድር አካላት ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝቦ የመስተዳድር አካላቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አድርጓል።
ጥገናው ተጠናቆ ወደአገልግሎት እስኪመለስ ድረስ ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቀም ጠይቋል።
እርዳታ ለሚፈልጉ ወገኖች ምን ያህል ድጋፍ እየተደረገ ነው ?
በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞን፦
- ኪረሙ፤
- ሁሙሩ እና አጋምሳ፣
- ቤጊ፤
- ጊዳሚ፤
- ቆንዳላ፤
- ሆሮ ሊሙ በተሰኙ ቦታዎች፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር እንዲሁም በትግራይና በአፋር ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ዜጎች ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸው፣ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሕልፈተ ሕይወት መድረሱ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የደረሰው መልዕክት ያስረዳል።
በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራና አፋር ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ረሃቡ እየተባባሰ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸው፣ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የድጋፍ ፈላጊዎቹን ጥያቄ ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ያቀረበ ሲሆን፣ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያና ተወካይ ዳይሬክተር አቶ አታለል አቦሃይ፣ "ወደ ዋግኽምራ፣ ወደ ሰሜን ጎንደር ድርቅ ያጠቃቸው አካባቢዎች ብዙ ጊዜ ትግራይን ጨምሮ አልሚ ምግብ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ነው ሲሰጥ የነበረው። እርሱ ከእርዳታው ከወጣ ስምንት ወራት አልፎታል የእርሱ መውጣት ተፅዕኖ ይኖረዋል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ድርቅ በተከሰተባችው አካባቢዎች ድጋፍ ለሚሹት ዜጎች ሁሉ እርዳታ ተደራሽ እንዳደረጉና እንዳላደረጉ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት አቶ አታለል፣ "አሁን የተላከው እህል እኮ ለአንድ ክልል በቂ ላይሆን ይችላል ግን የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ይማዳረስ ሥራ ነው እየሰራይ ያለነው" ሲሉ አስረድተዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያው አጠቃላይ እንደ አገር 20 ሚሊዮን ተረጂዎች እርዳታ ፈላጊ ሰዎች እንዳሉ ገልጸው፣ "ለ20 ሚሊዮኑ ሁሉ አድርሰናል አንልም" ነው ያሉት።
አክለውም፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ 20 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊዎች ሁሉ ድጋፍ ማድረስ ስለማይቻል የቅድሚያ ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸው ተብሎ ከየክልሉ ተለይተው በደብዳቤ ለተላኩ ተረጂዎች ሁሉ ግን ከአሥር ቀናት በፊትም ለ4 ሚሊዮን ሰዎች 610 ሺሕ ኩንታል እህል መላካቸውን ተናግረዋል።
አሁንም የቅድሚያ ቅድሚያ ተብለው የተለዩ እንዳሉ የጠቆሙት አቶ አታለል፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እርዳታ ቢያቆምም መንግሥት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደከዚህ ቀደሙ እርዳታ ለማድረግ ከመጣ የኮሚሽኑ ቢሮ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል በመጠለያ ጣቢያዎችና ድርቅ ተከስቶባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች፣ በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን፣ በዋግኽምራ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር፣ በኦሮሚያ ክልል በተለይ ወለጋ ዞን፣ በአፋር ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በከፋ ረሃብ ውስጥ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይነገራል።
ዩኒሴፍ በበኩሉ ጉዳዩን በተመለከተ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው ሪፓርት በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን፣ ከ942 ሺሕ በላይ ስደተኞችን፣ ከ16 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን ጨምሮ በአጠቃላይ የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር ከ34 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ማስታወቁ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያፈልጋቸው 34.4 ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ ከ674 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ፣ ከዚህም ውስጥ 345.4 ሚሊዮን ዶላር በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች፣ 255.7 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚደረግ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሆን፣ ይሁን እንጅ የተገኘው ገንዘብ 187.7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ሪፓርቱ ያስረዳል።
" እባክችሁ መፍትሄ ስጡን ፤ ጊዜው ያለ ትምህርት እየሄደብን ነው " - ተማሪዎች
በአማራ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሚማሩ ተማሪዎች እስካሁን ወደ ትምህርት እንዳልተመለሱ በመግለፅ ትምህርት ሚኒስቴር መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጥሪ አቀረቡ።
መልዕክታቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የላኩ ተማሪዎች እስካሁን የሚማሩባቸው ግቢዎች እንዳልጠሯቸው በማመልከት ያለ ትምህርት መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
በእነሱ እድሜና ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ የሚገኙ በሌሎች ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ጓደኞቻቸው ትምህርታቸውን ለመጀመር ወደ ሚማሩበት ተቋም ከበርካታ ቀናት በፊት መግባታቸውን እነሱ ግን እስካሁን መቼ እንኳን እንደሚጠሩ እንደማያውቁ በመግለፅ ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ መፍትሄ ቢሰጥ ብለዋል።
ተማሪዎቹ ከእኩዮቻቸው ወደ ኃላ እየቀሩ መሆኑን አመልክተው ይህም የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የፊልድ ምርጫ ካደረጉ በኃላ ወደቤት ተመልሰው ከወራት በላይ ያለትምህርት መቀመጣቸውን አመልክተዋል።
" ትምህርት ሚኒስቴር ስለኛ ጉዳይ ችላ ማለት የለበትም " ሲሉ ያሳስቡት ተማሪዎቹ የትግራይ ተማሪዎች አይነት ዕጣ ፋንታ እንዳይደርሰን ከወዲሁ አፋጣኝ መፍትሄ ይፈለግልን ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ፤ በአማራ ክልል ባለው ተለዋዋጭ የሆነ የፀጥታ ሁኔታ ከአማራ ክልል ወደ ተለያዩ ክልሎች ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሄደው መማር ያልቻሉ ተማሪዎች ስለመኖራቸው ለማወቅ ተችሏል።
ተማሪዎቹ በፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ለመሄድ መንገዶች ፈታኝ እንደሆነባቸው አመልክተዋል።
አቅም ያላቸው በአየር ትራንስፖርት ፤ አንፃራዊ ሰላም ያለባቸው ቦታዎች የሚኖሩ በብዙ ብር በየብስ ትራንስፖርት ወደ ሚማሩበት ተቋም መግባታቸውን ነገር ግን የፀጥታና ደህንነት ሁኔታው ባልተሟላባቸው በተለይ ጎጃም አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት መመለስ እንዳልቻሉ የደረሱን መልዕክቶች ያስረዳሉ።
ያለው የትራንስፖርት ዋጋም ውድ በመሆኑና መንገዶችም ስለሚያሰጉ እንደ " ቀይ መስቀል " አይነት ተቋማት እስካሁን ወደ ተቋማቸው ያልገቡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ተቋማቸው የሚወስዱበት መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቀዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ተወካይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑን ለቪኦኤ ሬድዮ ቃላቸውን ሰጥተው ነበር።
ዶ/ር ሰለሞን ፤ የደህንነት ችግር ካለባቸው አካባቢዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ ተቋማቸው የመመለሱ ስራ የሚሰራው ከወታደራዊ ኮማንድ ፖስት ጋር በመተባበር ነው ብለዋል።
" አሁን ባለው ሁኔታና ካለው የፀጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲዎች በሴኔት ተማሪዎችን የሚቀበሉበትን ቀን እየወሰኑ ተማሪዎችን እየጠሩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ ደግሞ እየተሰራ ያለው በዋናነት የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በአካባቢው ከሚገኙ የኮማንድ ፖስት አካላት ጋር በቅርብ እየተወያዩ ለተማሪዎች ካለው Safety እና Security አኳያ እየተገመገመ እየተሰራ እንደሆነ እናውቃለን " ብለዋል።
" እንደ ትምህርት ሚኒስቴርም ያለው concern ትክክለኛ ስለሆነ በቅርብ እየተከታተልን ነው። የሚፈለገው የድጋፍ እና ክትትል ስራ እየሰራን ነው። እስካሁን የጎላ ችግር አልቀረበም በኛ በኩል ቀጣይ የሚነሱ ችግሮች ካሉ በዛው ካለው የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ ሆነን እንሰራለን " ሲሉ ተናግረዋል።
#GAT የመቁረጫ ነጥብ ይፋ ሆነ።
" 62 (50%) እና በላይ ጥያቄዎችን የመለሱ / 80 ፐርሰንታይል ያገኙ በሚፈልጉበት ተቋም ገብተው መማር ይችላሉ "
የትምህርት ሚኒስቴር ለሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እና ለሁሉም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በፃፈው ደብዳቤ የአገራዊ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም የመግቢያ ፈተና (National GAT) የመቁረጫ ነጥብ አሳውቋል።
በዚህም መሠረት ፤ አጠቃላይ ከተፈተኑት ጥያቄዎች ውስጥ 62 (50%) እና በላይ ጥያቄዎችን የመለሱ ወይም 80 ፐርሰንታይል (80 Percentile) ያገኙ ተፈታኞች #ብቻ ለመማር በሚፈልጉበት ተቋም አመልክተው መማር የሚችሉ እንደሆነ ተገልጿል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመልካቾች ለማመልከት ሲመጡ ውጤታቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ https://portal.aau.edu.et/Web/ApplyForAdmission/TestingStatus በመግባት እና የተማሪውን የመግቢያ ስም (Username) እና የይለፍ ቃል (Password) በመጠቀም ማረጋገጥ ይቻላሉ ተብሏል።
በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት ፤ በሁሉም የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች በመንግስትና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ለመማር የሚፈልጉ አመልካቾች በሙሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የድህረ ምረቃ የመግቢያ ፈተና (National Graduate Admission Test-NGAT) ተፈትነው ያለፉ ብቻ መሆን እንዳለባቸው አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል።
(ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ/ም በትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ተፈርሞ የተላከው ደብዳቤ ከላይ ተያይዟል)
* ቲክቫህ ኢትዮጵያ የደብዳቤውን ትክክለኝነት ከትምህርት ሚኒስቴር አመራር ማረጋገጡን በዚሁ አጋጣሚ ያሳውቃል።
" አኲርፈው የተለዩትን በጠባይ ወደ እኛ እናምጣቸው ፤ እኛም ኲርፊያን ከሚያስከትል ድርጊት እንራቅ " - ቅዱስነታቸው
የጥቅምት ወር 2016 ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተከፈተ።
ምልዓተ ጉባኤው የተከፈተው ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር ነው።
ቅዱስነታቸው ምን አሉ ?
ቅዱስነታቸው ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር ወቅት ፤ ቤተክርስቲያኗ አሁን ለጀመረችውና ለወደፊትም ለምትጀምራቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች ዋስትና እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
" የስራዎቻችን ዋስትና በሀገርና በቤተክርስቲያን ፍጹም የሆነ ሰላምና አንድነት መኖር ነው " ብለዋል።
የጠማንን ሰላምና አንድነት መልሶ ለማምጣት የቤተክርስቲያን ኃይል የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ገልጸዋል።
ሆኖም የቤተክርስቲያን የሰላም ጉዞ ከማንኛውም #ወገንተኝነት_በጸዳ፣ ማእከሉና ዓላማው የሀገርና የቤተክርስቲያንን አንድነት ብቻ መሠረት ያደረገ መሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ከዚህ አንጻርም በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በቤተክርስቲያንም እንከን የለሽ አንድነት እንዲረጋገጥ በብርቱ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
" አኲርፈው የተለዩትን በጠባይ ወደ እኛ እናምጣቸው " ያሉት ቅዱስነታቸው " እኛም ኲርፊያን ከሚያስከትል ድርጊት እንራቅ። በአንድነት፣ በእኩልነትና በጋራ ሆነን ታላቋን ቤተክርስቲያን እንሰብስብ፣ እናገልግል፣ እንምራ፣ እንጠብቅ፡፡ ለዚህም ሙሉ ዝግጅት እናድርግ። " ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ፤ " የዕለት ተዕለት ስራችን የቤተክርስቲያንን ጭንቀት የሚያቃልል ይሁን " ያሉ ሲሆን " ይህ ከሆነ ቤተክርስቲያንን ያለ ምንም ጥርጥር በዕድገት ጐዳና ወደ ፊት እናሻግራለን " ሲሉ ገልጸዋል።
የታላቋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መርምሮ ገምግሞና አጥንቶ ችግር ፈቺ ውሳኔን የመስጠት ኃላፊነት ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑንም ቅዱስነታቸው በቤተክርቲያን ስም አብስረዋል።
(የቅዱስነታቸው ሙሉ ንግግር ከላይ ተያይዟል)
#እንድታውቁት
የነዳጅ ዋጋ ባለበት ይቀጥላል።
ከጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ቀደም ሲል በስራ ላይ በነበረበት ዋጋ እንደሚቀጥል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
ቀደም ሲል የነበረው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ስንት ነው ?
- ቤንዚን በሊትር 77 ብር ከ65 ሳንቲም
- ነጭ ናፍጣ በሊትር 79 ብር ከ75 ሳንቲም
- ኬሮሲን በሊትር 79 ብር ከ75 ሳንቲም
- ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 62 ብር ከ36 ሳንቲም
- ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 61 ብር ከ16 ሳንቲም
ምንጭ፦ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር
ምንም አይነት ግብይት ሳይኖር ደረሠኝ ሲሸጥ የነበረ ግለሰብ በ12 ዓመት እስራት እና በ126 ሺህ ብር ገንዘብ መቀጣቱ ተነገረ።
ከአዲስ አበባ ፖሊስ በተገኘ መረጃ ፤ ተከሳሹ በሱፍቃድ ሳህሉ ይባላል፡፡
የወንጀል ድርጊቱን ሲፈፅም የነበረውም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልደታ ኮንዶሚንየም በተከራየው ቤት ውስጥ መሆኑ ተመላክቷል።
ግለሰቡ በሃሰተኛ ንግድ ፈቃድ የወጡ የሂሳብ መመዝገቢያ ማሽኖችን በቤቱ አስቀምጦ ምንም አይነት ግብይት ሳይኖር ግብይት የተፈፀመ በማስመሰል ለግለሰቦች ደረሰኝ ሲሸጥ እንደቆየ ተገልጿል።
የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖቹ በሃሰተኛ ሰነድ የወጡ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ በእነዚህ ማሽኖች የሚፈፀም ግብይት ህገ ወጥ ስለመሆኑ በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ እና በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር በተበተነ ሰርኩላር ማሽኖቹ አገልግሎት እንዳይሰጡ የታገዱ ስለመሆናቸው መረጃው ያሳያል።
ፖሊስም በደረሰው ጥቆማ እና ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ/ም ተጠርጣሪው ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ባደረገው ብርበራ ፦
- አምስት የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖች፣
- ሽያጭ የተከናወነባቸው በርካታ የዜድ ሪፖርት ወረቀቶች፣
- ለወንጀል ተግባሩ ስራ ላይ የሚውሉ ኮምፒውተሮች ፕሪንተር እና ሃሰተኛ የንግድ ፈቃዶች መያዛቸው ተመላክቷል።
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጉዳዩን ሲመለከት ቆይቶ ሰሞኑን በዋለው ችሎት የተከሳሽ በሱፍቃድ ሳህሉን ጥፋተኝነት በማረጋገጥ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ126 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
መረጃው የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው።
#Hawassa
" ለአራት ቀን ያለምንም ወንጀል የታሰሩበት ምክንያት በፋጣኝ ምላሽ ይሰጥበት። " - የታሳሪ ቤተሰብ
" በእስር ላይ የሚገኙ አሸከርካሪዎች ከእስር ተለቀዉ ወደ ስራ ይመለሳሉ ፤ ሁሉም ነገር በህግና በደንብ እየተመራ ይቀጥላል " - የሀዋሳ ከተማ መንገድ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት
ወደ ሀዋሳ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ቅሬታቸዉን ለማቅረብ የተንቀሳቀሱ በርካታ የባጃጅ አሽከርካሪዎች መታሰራቸዉ ተሰማ።
አንድ የታሳሪ ቤተሰብ ነኝ ያሉ ግለሰብ ፤ " በሀዋሳ ከተማ እለተ አርብ በጠዋት፣ በተለምደው የሺ ከብልስቶን መንገድ በሚባል መንገድ ላይ የባጃጅ ሾፈሮች ከመንገዱ እና ካላቸው የስምሪት ጥያቄ የተነሳ ቅሬታ ለማቅረብ ወደ መንገድ እና ትራሰንፖርት አቅንተው ነበር " ብለዋል።
" እኚሁ የባጃጅ ሹፌሮች ጥያቄያቸውን ለማቅረብ በሄዱበት በፖሊስ ተከበው ወደ 80 የሚጠጉ የባጃጅ ሾሬሮችን በየክፍለከተማው አስር አስር እየተደረጉ በፓትሮል ተወስደው ታስረዋል " ያሉት እኚሁ ግለሰብ " ይህ የተፈፀመው አርብ ፣ ቅዳሜ እሁድ እና ሰኞን ጨምሮ ነው " ብለዋል።
" የተሰራ ወንጀልም ይሁን የተሰማ ድምፅም የለም " የሚሉት የታሳሪው ቤተሰብ " የታሰሩት ሰዎች እስካሆን ጉዳያቸውን የሚያነሳ አካልም የለም፣ በምን ጉዳይ ላይ እንደታሰሩም የተሰጠም ማብራሪያም የለም፣ ተዳፍነው እስር ቤት ናቸው " ብለዋል።
" የሲዳማ ክልል ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ይሄን ጉዳይ ያውቀው ይሆን ? " ሲሉ የጠየቁት ግለሰቡ " አይደለም 80 አንድ እስረኛ በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ነው ህጋችን። ለአራት ቀን ያለምንም ወንጀል የታሰሩበት ምክንያት በፋጣኝ ምላሽ ይሰጥበት። " ብለዋል።
ይህንን እና በውስጥ የመጡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ሀዋሳ አባል የባጃጅ ሹፌሮችን አነጋግሯል።
ያነጋገራቸው የባጃጅ ሹፌሮች ባጃጆችን ከዋና ዋና መንገዶች የማስወጣት እንቅስቃሴ በከተማዉ ዳርቻም ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ የነዳጅ ፣ የመለዋወጫና የኑሮ ሁኔታዉን ያላገናዘበ ታሪፍና ድንገተኛ ስምሪት እየተጣለብን ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
ከሰሞኑን ከአቶቴ - ንግስተ ፉራ የነበረዉ ርቀት ድንገት በመቀየሩ የተፈጠረዉን አለመግባባት በዉይይት ለመቅረፍ ወደመንገድ ትራንስፖርት የተመረጡ አሽከርካሪዎች መሄዳቸዉን ተከትሎ ለእስር መዳረጋቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የሀዋሳ ከተማ መንገድ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ምክትል የመምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ አዴላ ፤ ችግሩ የተከሰተዉ የትራፊክ ፖሊስ የስምሪት ቦታዉን በመለወጣቸዉና አሽከርካሪዎች አዲሱን ርቀት አንቀበልም በማለት በተነሳ ግጭት መሆኑን ጠቅሰዉ አሁን ላይ ስምሪቱን የከተማዉ መንገድ ትራንስፖርት ብቻ እንደሚሰጥ መተማመን ላይ በመድረሱ ችግሩ ተቀርፏል ብለዋል።
ምክትል ኃላፊዉ ፤ በእስር ላይ የሚገኙ አሸከርካሪዎች ከእስር ተለቀዉ ወደ ስራ እንደሚመለሱ ገልጸው ሁሉም ነገር በህግና በደንብ እየተመራ እንደሚቀጥል አስገዝበዋል።
#NEBE
በገዛ ፍቃዳቸው ከኃላፊነታቸው በለቀቁት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምትክ አዲስ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ለመተካት 8 አባላት ያሉት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ዕጩ መልማይ ኮሚቴ ዛሬ ተሰይሟል።
ይኸው ኮሚቴ የተሰየመው በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ነው።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 102 እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133/2011 አንቀፅ 5/1 ላይ በሰፈረው መሰረት #ጠቅላይ_ሚኒስትሩ ዕጩ የስራ አመራር ቦርድ አባላት የሚመለምል ገለልተኛ ኮሚቴ እንደሚሰይሙ ይደነግጋል።
የተቋቋመው መልማይ ኮሚቴ ወደ ስራ መግባቱ የተነገረ ሲሆን በቅርቡ #ጥቆማ መቀበል እንደሚጀምር ተገልጿል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሰቢ መልማይ ኮሚቴው ፦
- ቀሲስ ታጋይ ታደለ (ሰብሳቢ)
- ፕ/ር ተከተል ዮሐንስ (አባል)
- አቶ ባዩህ በዛብህ (አባል)
- ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ (አባል)
- አቶ ካሳሁን ፎሎ (አባል)
- ወይዘሮ ርግበ ገብረሃዋርያ (አባል)
- ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ (አባል)
- ኢ/ር መላኩ እዘዘው (አባል)
መረጃው ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት የተገኘ ነው።
አንድ ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፣ ህወሓት እና ሀገራት ምን አሉ ?
የኢትዮጵያ መንግሥት
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ የፕሪቶሪያው ግጭት የማስቆም ስምምነት ዋና ዉጤት " የጦር መሣሪያ ላንቃ መዘጋቱ " እንደሆነ አሳውቋል።
ሚኒስቴር ከግጭት ማቆሙ ስምምነት በኋላ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የምትጠቀስበት ሁኔታ ካለፈው ዓመት የተለየ ሆኗል ብሏል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ ከተለያዩ ሀገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት መለወጡን የግለፀው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከአየርላንድ እንዲሁም ከአውሮጳ ሕብረት/EU ጋር ያላትን ግንኙነት እንዲሻሻል ማድረጉን እንደ ማሳያ ገልጿል።
ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ምን አስገኘ ለሚለው ጥያቄም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር " ሰላም አስገኝቷል " ሲሉ ምላሽ ሰጥቷል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ ምንም እንኳን በተደረሰው ስምምነት ግጭት በመቆሙ ሻክረው የነበሩ ግንኙነቶች አሁን መልካቸውን ቢቀይሩም የምልሶ ግንባታ እና የጦርነቱ ሰለባዎችን መልሶ በማቋቋም ረገድ እጥረት መኖሩን አልሸሸገም ሲል ዶቼ ቨለ ዘግቧል።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር
በአሁን ሰዓት ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የስምምነቱ ፈራሚ ህወሓት በየፊናቸው የሰላም ስምምነቱን አንደኛ አመት አስመልክተው መግለጫ አውጥተዋል።
ጊዚያዊው አስተዳደሩ በመግላጫው ላይ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ህዝቡን ለማጥፋት ሲካሄድ የነበረን ዘመቻ እንዲሁም እንደ ብሄር ትግራዋይ እንዲጠፋ የህዝቡ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ከሰዎች ህሊና ሳይቀር እንዲሰረዝ የተጎነጎነ ሴራ እንዲገታ አድርጓል ብሏል።
ስምምነቱ ሁሉም ፍላጎቶች እና ወደ ጦርነት ያስገቡ ጠንቆች በተቻለ መጠን ሰላማዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ሊሳካ ይችላል የሚል በር መክፈቱን አመልክቷል።
ስምምነቱ አንድ አመት ቢሞላውም እስከ አሁን ድረስ ነፃ ያልወጣ ህዝብ ነፃ የማውጣት ፣ የተፈናቀለ ወደ ቄየው የመመለስ ፣ ህገ-መንግስታዊና ሉአላዊ የትግራይ ግዛት የማረጋገጥ ጉዳይ ፈፅሞ አልተነካም ፤ አሁንም ህዝቡ መከራ ውስጥ እየኖረ ነው ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ አመልክቷል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶሪያው የሰላም ውል በዓለም ማህበረሰብ ፊት የተፈፀመ ስምምነት እንደመሆኑ መጠን ፣ የዓለም ማህበረሰብ በአፈፃፀሙ ያሉ እንቅፋቶች በማስወገድና የትግራይ ህዝብ ኑሮ ወደ ነበረበት የመመለስ ህጋዊና ሞራላዊ ግዴታውን እንዲፈፅም ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ህወሓት
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ( #ህወሓት ) በፊናው ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ የዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መሰረት መሆኑን ገልጿል።
ለስምምነቱ ተፈፃሚነት አባላቱና ደጋፊዎቹ በማሳተፍ በቁርጠኝነት እየታገለ መቆየቱንና ትግሉ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።
" የስምምነቱ ፈራሚ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት በውሉ ላይ የተቀመጡ ወሳኝ መሰረታዊ አበይት ጉዳዮች በአግባቡ አልፈፀመም " ያለው ህወሓት " ይህንንም የዓለም ማህበረሰብ የሚያውቀው ሃቅ ነው " ሲል ገልጿል።
" በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እስከ አሁነ የተገኙት ድሎች በማክበር ፤ የተቀሩት እንዲፈፀሙ የፌደራል መንግስት በውሉ መሰረት ሃላፊነቱ መፈፀም ይገባዋል ፤ ውሉ እንዲፈረም ሚና የነበራቸው ሁሉም አካላት ኢጋድ ፣ የአፍሪካ ህብረት ፣ የአሜሪካ መንግስት ፣ የአውሮፓ ህብረት ፣ ተሰሚነት ያላቸው የሰብአዊ መብት ተማጓቾችና የሚድያ ተቋማት እንዲሁም የዓለም ማህበረሰብ ሞራላዊና ፓለቲካዊ ሃላፊነታቸው መወጣት ይገባቸዋል " ሲል ህወሓት በመግለጫው አስገንዝበዋል።
ሀገራት ምን አሉ ?
መቀመጫቸው አዲስ አበባ የሆኑ #የአስር_ሀገራት ኤምባሲዎች በኢትዮጵያ ለ2 ዓመታት ተካሂዶ በነበረው ግጭት ተሳትፈው የነበሩ ሁሉም ወገኖች የሰላም ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና አሉ ያሏቸውም ተግዳሮቶች በንግግር መፍትሄ እንዲያገኙ ጥሪ አድርግዋል።
- አውስትራሊያ፣
- ካናዳ፣
- ዴንማርክ፣
- ፊንላንድ፣
- ጃፓን፣
- ኔዘርላንድስ፣
- ኒውዚላንድ፣
- ኖርዌይ፣
- ስውዲን፣
- ዩናይትድ ኪንግደም/ዩኬ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተካሄደ ወዲህ በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች ሰላምን ለማምጣት ያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል።
ስምምነቱ የተፈረመበት #አንደኛ_ዓመት ፣ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶች የሚደነቁብት እንዲሁም ደግሞ ተግዳሮቶች እንዳሉ እና የተሟላና አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ ጥረቶች በእጥፍ መቀጠል እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚወሠድበት መሆኑን ኤምባሲዎቹ አመልክተዋል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የጀመረው ደም አፋሳሹ ፣ እጅግ አውዳሚና አስከፊው መነሻውን ትግራይ አድርጎ ወደ አጎራባችን ክልሎች የተዛመተው ጦርነት ከ2 አመት በኃላ ህወሓትና የፌደራል መንግስት በደቡብ አፍሪካዋ የፕሪቶሪያ ከተማ ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም በፈረሙት ግጭት ማቆም ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ባካተተ የሰላም ስምምነት ውል ጦርነቱ መቋጫ ማግኘቱ ይታወሳል ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ዘግቧል።
መምህራን ምን አሉ ?
• " የመምህራን ደመወዝ ይቆረጣል የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ አሳማኝ አይደለም "
• " የፌዴራል መንግሥት የዓመቱን በጀት ወደ ክልሎች ቢልክም፣ ክልሎች ለወረዳዎች አይልኩም "
• " አንዳንዴ ደመወዝ ለበርካታ ወራት ሳይከፈላቸው ይጠብቃሉ፤ ግማሽ ደመወዝ ብቻ የሚከፈልበት ጊዜም አለ "
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በጅግጅጋ ከተማ ባካሄደው 36ኛው ጉባዔ ላይ፣ በክልሎች የበርካታ መምህራን ደመወዝ ያላግባብ እንደሚቆረጥ በስፋት መነሳቱ ተገልጿል።
የማኅበሩ ጉባዔ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከሲዳማና ከሌሎቸም ክልሎች መምህራን ደመወዛቸው ያላግባብ እንደሚቆረጥ በስፋት መነሳቱን በስብሰባው የተሳተፉ የማኅበሩ አመራሮች ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል ጳውሎስ እንደገለጹት፣ በክልሉ እስከ 60 በመቶ የሚደርስ የመምህራን ደመወዝ እንደሚቆረጥና ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት አሳማኝ አይደለም ብለዋል።
የፌዴራል መንግሥት የዓመቱን በጀት ወደ ክልሎች ቢልክም፣ ክልሎች ለወረዳዎች እንደማይልኩ፣ በጀቱ ለማዳበሪያ ክፍያ ዋለ በሚል ወደ መምህራን ሳይደረስ እንደሚቀር መምህራን መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
አንዳንዴ ደመወዝ ለበርካታ ወራት ሳይከፈላቸው እንደሚጠብቁና ግማሽ ደመወዝ ብቻ እንደሚከፈላቸውም ተነግሯል፡፡
መንግሥት በአንድ በኩል ስለትምህርት ጥራት እየተናገረ፣ በሌላ በኩል የመምህራን ደመወዝ እንደማይከፈል፣ የደረጃ ዕድገትና የትምህርት ማሻሻያ እንደማይደረግ በጉባዔው ላይ መነጋገሪያ ነበር ተብሏል፡፡
የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እንዳሉት፣ በክልሉ በርካታ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ውስን መሆናቸውን፣ የበጀት እጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃቸው መምህራን በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ለሚከናወን ሥራ ከ2017 ዓ.ም. በጀት መበደራቸው ተገልጿል፡፡
ማኅበሩ በጅግጅጋ ባከሄደው ወይይት የመምህራኑ ጉዳዩ በስፋት መነሳቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለዚህ ችግር ክልሎች ጉዳዩን በባለቤትነት ወስደው መፍትሔ እንዲፈልጉ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) መናገራቸውን፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ከሚኒስትሩ ጋር በነበረው ውይይትም ማኅበሩ ከዚህ ቀደም በደብዳቤና በሪፖርት መልክ ሲያቀርባቸው የነበሩ ጥያቄዎችን፣ የትምህርት ሚኒስትሩን በአካል በማግኘት የመምህራኑን ሕይወት ሊቀይሩ የሚችሉ ጥያቄዎች ተነስተው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል ብለዋል፡፡
በሁሉም ክልሎች የሚገኙ መምህራን በጉባዔው የኑሮ ሁኔታቸው እንዲሻሻል ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበው ሚኒስትሩ እንደ ሁኔታው እየታየ ወደፊት የመምህራኑን ሕይወት ሊቀይር የሚችል ሥራ ይከናወናል ማለታቸውን ዮሐንስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ከአፋር ክልል ተፈናቅለው ወደ ትግራይ ክልል የሄዱ 500 መምህራን ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ምክክር ተደርጎበታል ብለዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም. ክረምት ተቋርጦ የነበረው የመምህራን የክረምት ትምህርት እንዲቀጥል ስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ጉባዔውን በተመለከተ ሚኒስትሩን ጠቅሶ በድረ ገጹ እንዳሠፈረው፣ አገሪቱ አሁን ላለችበት አገራዊ ችግር የትምህርት ሥርዓት መውደቁ ምክንያት በመሆኑ፣ የመምህራን ማኅበር ችግሩን ተነጋግሮ መፍታት እንዳለበትና ማኅበሩ የሙያውን ክብር ለመመለስ ከኅብረተሰቡ ጋር ወይይት በማድረግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የዚህ መረጃ ባለቤት ሪፖርተር ጋዜጣ ነው።
" መንግስት የሚወስነውን የሆነ አካል ተነስቶ ' ይህ ይሁን ፤ ይህ ደግሞ አይሁን ' ማለት ትክክል አይደለም " - አቶ ረዳኢ ኃለፎም
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ " ወቅቱን ያልጠበቀና ህገወጥ ነው " በማለት እንዳይካሄድ ክልከላ ያስተላለፉበት የህወሓት የካድሬዎች ስብሰባ የአጠራሩን አግባብነት ከተነጋገሩበት በኃላ ፓርቲው ያጋጠሙትን አደጋዎች አስመልክቶ ባፀደቀው ዋና አጀንዳ ላይ ከ2 ሳምንት በኃላ ተገናኝቶ ለመወያየት ወስነው ተበትነዋል።
ምንም እንኳን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልከላ ቢጥልም የህወሓት ካድሬዎች ቅዳሜና እሁድ መቐለ ሰማዕታት አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ነበር።
የስብሰባው መጠናቀቅን ተከትሎ ፓርቲው ባሰራጨው መግለጫ ፤ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አስቀድሞ ካድሬዎችን ሰብሰበው ባለማናገራቸው ወቅሷል።
በፓርቲው ላይ ያጠላው አደጋ ምንድነው ? በሚል በተቀረፀ ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ ላይ ችግሩን በተረጋጋ መንፈስ ለመገምገምና የውስጥ ማጥራት ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን ፓርቲው ገልጿል።
በዶክተር ደብረፅዮ ገ/ሚካኤል የተመራው የፓርቲው የካድሬዎች ስብሰባ የስብሰባው ዋና አጀንዳዎች በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከሁለት ሳምንታት በኃላ እንዲታዩ ውሳኔውን አሳልፎ ተበትኗል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ በፓርቲው ካድሬዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ተቋማዊ አሰራርን ያልተከተለ ነው በሚል የተቸው ፓርቲው እርምት እንዲደረግ ጠይቋል።
ባለፈው ሳምንት ከመንግስት የስራ ኃላፊነት ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 6 ከዞን አመራሮች ከአቶ ጌታቸው ረዳ በተላከላቸው ደብዳቤ ከስልጥን እንዲነሱ መደረጉ አይዘነጋም።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምን አለ ?
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ረዳኢ ኃለፎም ስብሰባው እንዳይካሄድ ያገድነው ተሳታፊዎቹ የመንግስት ሰራተኞች እና አመራሮች እንደመሆናቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ቅድሚያ የሰጣቸው ተግባራት በመኖራቸው ነው ብለዋል።
አቶ ረዳኢ ሃለፎም ፦
" ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስብሰባው ትክክል አይደለም ያለው በአሁን ሰዓት መሰራት ለሚገባቸው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርት ላይ ጉዳት ሳያደርስ የመሰብሰብ እና አንበጣን የመከላከል ተግባራት የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጡ ነው።
ይኸውም ቅድሚ እንዲሰጠው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን በህወሓት መሪዎችም ጭምር መግባባት ላይ ተደርሶ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ስለተወሰነ ነው።
ስብሰባው የተካሄደው ከዚህ የጋራ ውሳኔ በኃላ ነው። መንግስት የሚወስነውን የሆነ አካል ተነስቶ ' ይህ ይሁን ፤ ይህ ደግሞ አይሁን ' ማለት ትክክል አይደለም።
ከኃላፊነት የተነሱት ሰዎች ከአሁን በፊት የተመደቡት በስብሰባ አይደለም፤ ከስራ ቦታ ሲነሱም በስብሰባ አይሆንም። በስብሰባ እገሌን መድቡት እገሌን ደግሞ አቆዩት ማለት ትክክል አይደለም።
ሹመት በሚገባቸው ቦታዎች ላይ ሰዎች ይሾማሉ ከስራ ምድብ ማንሳት በሚያስፈልግበት ጊዜ ደግሞ ይነሳሉ። ከዚህ ውጭ ያለው ስክነትና ማስተዋል የጎደለበት ጩኸት ነው። "
የዚህ መረጃ ባለቤት ቪኦኤ ሬድዮ ጣቢያ መሆኑን እንገልፃለን።
#ጥቆማ #ከጠቀማችሁ
☑ የአዳማ ጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ተወርሰው የሚገኙ 171 ተሽከርካሪዎችን በግልፅ ጨረታ ባሉበት ሁኔታ አወዳድሮ መሸጥ ይፈልጋል። ተጨራቾች የጨረታ ሰንድ በመግዛት በጨረታው ላይ የሚወጡትን ተሽከርካሪዎች በአካል በመመልከት መጫረት ትችላላችሁ ተብሏል። ጨረታው በ26/02/2016 ዓ/ም ጥዋት 4 ሰዓት ላይ የጨረታ ሳጥኑ ተዘግቶ በዚሁ ቀን 4:15 ላይ የጨረታ ሳጥኑ ይከፈታል። ለተጨማሪ መረጃ በስልክ 0221118429 ላይ መወደል ይቻላል።
☑ አዲስ አበባ ቃሊት ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት የተተው፣ የተወረሱ እና በኮንትሮባንድ ተይዘው የሚገኙ የተለያዩ የቤትና የጭነት ተሸከርካሪዎች ፦
- DUMP TRUCK፣
- IVECO FIAT፣
- TOYOTA HAILUX፣
- TOYOTA COROLLA፣
- TOYOTA VITZ፣
- TOYOTA HAICE፣
- TOYOTA YARIS፣
- TOYOTA CHR፣
- HYUNDAI፣
- SUZUKI፣
- MISTUBUSHI ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን፣ የሞባይል ክፍሎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን፣ የተለያዩ የተዘጋጁ አልባሳትና ጫማዎች፣ የውብት መጠበቂያ ዕቃዎች እና ሌሎች የተለያዩ ዕቃዎችን ባሉበት ሁኔታ በግልፅና በሃራጅ ጨረታ አወዳድሮ ለመሸጥ ይፈልጋል። የተጠቀሱት ተሸከርካሪዎች የጨረታ ሰነድ ከቀን 20/02/2016 ዓ.ም ጀምሮ ማግኘት ይቻላል።
(ዝርዝር መረጃዎችን ከላይ በምስሉ ይመልከቱ)
☑ የገቢዎች ሚኒስቴር በታክስ ዕዳ የያዛቸውን ተሽከርካሪዎችና ሌሎች የተለያዩ ንብረቶች ለመሸጥ ይፈልጋል።
ከፎኔክስ ኢንደስትሪ ኃ/የ/የግ/ማህበር የተያዘ፦
- የኘላስቲክ ወንበር ማምረቻ ማሽን፣ የማሽኑ ማቀዝቀዣ (cooler)፣ የማሽኑ ጥሬ ዕቃዎችና ሌሎች ተጓዳኝ ዕቃዎች፣
ከተክለብርሃን አምባየ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማህበር የተያዙ ፦
- የተለያዩ መጠን ያላቸው የመብራት አምፖሎች፣
- ፍሎረሰንቶች፣
- ፖውዛዎች እና የውሃ ተቀባሪና ተንጠልጣይ የተለያዩ ቧንቧዎች፣
🚘 ከቲ.አይ.ቢ ኬተሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህ እና ኦክስፎርድ አማልጌትድ ኃ/የተ/ የግ/ማህበር የተያዙ የተለያየ ሞዴል ያላቸውን 3 ተሽከርካሪዎች ናቸው።
(ዝርዝር መረጃዎችን ከላይ በምስሉ ይመልከቱ)
#ጉምሩክኮሚሽን #አዲስዘመን #ገቢዎችሚኒስቴር
#እገታ
ከ3 ሳምንት በፊት መስከረም 20/2016 ዓ/ም ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ከባቱ ከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው የአሉቶ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ሲጓዙ በታጣቂዎች ከታገቱት 6 ሰዎች ውስጥ 3ቱ ቢለቀቁም ሌሎች 3 ሰዎች ደግሞ እስካሁን እንደታገቱ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ስማቸው ይፋ እድንዳይሆን ጠይቀው መረጃ የሰጡ የፕሮጀክቱ ሰራተኛ ታጋቾቹ እያንዳንዳቸው በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ እንደተጠየቀባቸው / በድምሩ የተጠየቀው 60 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረው ነበር።
ከታጋቾቹ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ትላንት ቃላቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን ፤ ታጋቾቹን የማስለቀቅ ጥረት መቀጠሉን በማስረዳት እስካሁን 3ቱን ማስለቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።
" ግማሾቹ ተለቀዋል፡፡ የተቀሩትንም ለማስለቀቅ ጥረቶች ቀጥለዋል " ያሉት አቶ ሞገስ ተለቀዋል የተባሉ 3ቱ ሰራተኞች በምን አይነት መንገድ እንደተለቀቁና የተቀሩት 3ቱ ደግሞ ለምን ሳይለቀቁ ቀሩ የሚለውን ጥያቄ ለታጋቾቹ ደህንነት በሚል ሳያብራሩት ቀርተዋል፡፡
ከእገታ ነፃ ከወጡት ውስጥ አንደኛው #ኬንያዊ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቱ ሰራተኞች እንዲሁም የታጋች ቤተሰቦች እገታውንና የተለቀቁትን ታጋቾች በተመለከተ " ለደህንነታችን መልካም አይደለም " በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት አልፈለጉም።
ፌዴራል ፖሊስ ስለ ተስፋፋው የ #እገታ ተግባር ምን ይላል ? እገታን ለማስቀረት መንግሥት ምን እየሰራ ነው ?
የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ አቶ ጄኢላን አብዲ ችግሩን ከመሰረቱ ለመከላከል ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ያሻዋል ብለዋል።
" እገታን ሰራዊት በማዘዝና ኮማንድ በመስጠት ሙሉ በሙሉ የምንከላከለው አይደለም፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ተደብቀው እንደዚህ አይነት ድርጊት ሚፈጽሙ አካላት አሉ፡፡ " ሲሉ ገልጸዋል።
" ህዝብ ጋር ተባብረን መረጃ ስንቀበል አስቀድመን ያስቀረነውም ሆነ ያስለቀቅናቸው እገታዎች አሉ፡፡ " ያለቱ አቶ ጄይላን " ህብረተሰቡ ነው መጠቆም ያለበት እደዚህ አይነት ነገሮችን፡፡ " ብለዋል።
° ህብረተሰቡ ጥቆማዎችን በሚሰጥበት ወቅት ከአጋቾች ለሚደርስበት ጥቃት ምን ያህል የማምለጥ ዋስትና ይኖረዋል ? የጸጥታ ኃይሉ በፍጥነት የመድረስ ሁኔታ ላይ ጥያቄ አይነሳም ወይ ? የተባሉት የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ፦
" ከህብረተሰቡ ራሱ ጥንቃቄ የጎደሉ አካሄዶች ይስተዋላሉ፡፡
ለምሳሌ መሬት ትገዛለህ ይህን ያህል ብር ይዘህ ና ተብለው የታገቱ አሉ፡፡ እገታ ድንገት በአጋቾች የሚፈጸም እንደመሆኑም እያንዳንዱን ነገር መከላከል አዳጋች ነው፡፡
እገታ ደግሞ ሳይጠበቅ ቶሎ የሚፈጸም ተግባር ስለሆነ ቶሎ ለመቆጣጠር አመቺ አይደለም፡፡ " ሲሉ መልሰዋል።
አቶ ጀኢላን ፤ ፖሊስ ጥቆማ ከደረሰው ቶሎ ወንጀሉ የተፈጸመበት ስፍራ በመድረስ እርምጃ ለመውሰድ ሚያስችል የተሸለ ቴክኖሎጂ አለው ያሉ ሲሆን በየስፍራው ፖሊሶችም እንዲኖሩ የሚያስችል የቁጥጥር ስርኣት መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡
አሁን አሁን በአደንዳዥ እፆች የሚደገፍ የእገታ ወንጀል በተለይ #በከተሞች መበራከታቸውንም ያስገነዘቡት አቶ ጀኢላን " ወንጀሉ ከተፈጸመም በኋላ በርካታ ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው " ሲሉ ተናግረዋል።
እገታ በሚፈጸምበት ጊዜ ፖሊስ የራሱ ወታደራዊ ስልት የሚጠቀም ይሆናል እንጂ ከአጋጆች ጋር በምንም አይደራደርም ያሉ ሲሆን ይህን በሚያደርጉ ተቋማት ተግባር ላይ ማብራሪያ እንደማይሰጡ ገልጸዋል።
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የጀርመን ድምፅ ሬድዮ / ዶቼ ቨለ ነው።
#ድሬዳዋ
🔹" የትውልድን ስነምግባር የምትቀርጽ እና በይዞታዋም ህጋዊ የሆነችን ቤተክርስቲያን አፍርሶ ሆቴል መስራት አግባብነት የለውም " - ቤተክርስቲያን
🔸" ቦታውን ለልማት ተፈልጎ ነው ፤ ካቢኔው የልማት ጥያቄዎችን የማስተናገድ ሃላፊነት አለበት " - የድሬዳዋ ከንቲባ ጽ/ቤት
የድሬደዋ መካነ-ኢየሱስ ቤተክርስቲያን የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ቤተክርስቲያኗ ካለችበት ቦታ እንድትነሳ የሚል ደብዳቤ እንደላከላት አስታውቃለች።
ቤተክርስቲያኗ የከተማው አስተዳደር ውሳኔውን በ2 ቀን ውስጥ እንዲያስተካክል ጠይቃለች።
ቤተክርስቲያኗ ፤ ለ40 አመታት በስፍራው የቆየች እና ህጋዊ ይዞታ እንዳላት የገለፀች ሲሆን የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ግን ለሆቴል ስራ በሚል በአንድ ወር ውስጥ ከቦታው እንድትነሳ ደብዳቤ መላኩን አስረድታለች።
የቤተክርስቲያኗ ዋና ሰብሳቢ ቄስ በላቸው አምባሮ ፤ " የከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት ለቤትክረስቲያኗ በላከው ደብደቤ እንዳስቀመጠው ቦታው ለሆቴል ቱሪዝም መፈለጉን የሚገልፅ ነው " ብለዋል።
ነገር ግን የትውልድን ስነምግባር የምትቀርጽ እና በይዞታዋም ህጋዊ የሆነችን ቤተክርስቲያን አፍርሶ ሆቴል መስራት አግባብነት የሌለው እና በምዕመን መካከል ሁከትን መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
" ከዚህ በፊት ቤተክርስቲያኗ ለከተማዋ መንገድ ስራ በሚል ተባበሪ በመሆን የተወሰኑ ሜትሮችን ወደ ውስጥ ተጠግታለች " ያሉት ቄስ በላቸው፣ " ይህ ግን በህልውናዋ ላይ የመጣ ነው " ብለዋል፡፡
ስለሆነም የከተማዋ ከንቲባ ጽ/ቤት ካቢኔ የወሰነውን ውሳኔ በሁለት ቀን ውስጥ እንዲያስተካክል የጠየቁ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ቤተክርስቲያኗ ሌሎች ህጋዊ አማራጮችን እንደምትጠቀም አስገንዝበዋል።
የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ ጸህፈት ቤት በበኩሉ ቤተክርስቲያኗ እንድትናሳ ካቢኔው ወስኖ ለቤተክርስቲያኗ ደብዳቤ መላኩን አረጋግጧል።
የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ፤ " ቦታው ለልማት ተፈልጎ ነው ፤ ካቢኔው የልማት ጥያቄዎችን የማስተናገድ ሃላፊነት አለበት " ብለዋል።
ነገር ግን ቤተክርስቲያኗ ጉዳዩን ተቃውማ ደብዳቤ ከመላክ ውጭ ከጽ/ቤቱ ጋር አልተነጋገረችም ያሉ ሲሆን ሁሉም ነገር የሚፈታው በንግግር ነው ብለዋል።
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ሬድዮ ጣቢያ ነው።
#ENDF🇪🇹
በሀገር ደረጃ ዛሬ 116ኛው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ተከብሯል።
ለመሆኑ በዓሉ ለምንድነው " ለ116ኛ ጊዜ " እየተባለ የሚከበረው ?
ይህ ቀን / ጥቅምት 15 የተመረጠው ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1900 ዓ/ም ያቋቋሙትን የጦር ሚኒስቴርን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ከዚህ ቀደም የ " መከላከያ ሰራዊት ቀን " ተብሎ ሲከበር የነበረው ኢህአዴግ በ1987 ዓ/ም አዲስ የመከላከያ ሰራዊት ማቋቋሚያ አዋጅ አዘጋጅቶ በተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀበት ወቅት ነው።
በዚህ መነሻ የካቲት 7 ቀን በየዓመቱ ሲከበር ነበር።
ኢህአዴግ በውስጡ የነበሩት አመራሮች አጠቃላይ ሀገራዊ ለውጥ ካደረጉ በኃላ / በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የሀገር አስተዳደር የቀድሞው ውሳኔው " ከ1987 በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ ሰራዊት እና የዘመኑ ትውልድ ተጋድሎን ውድቅ ያደረገና ቆርጦ ያስቀረ ነው " በማለት ቀኑን ወደ ጥቅምት 15 ቀይሮታል።
ቀኑ እንዲቀየር በተደረገው ጥናት ለበዓሉ መከበር መነሻ የሀገር ሰራዊት በቋሚነት ተደራጅቶ እንደ ተቋም የተመሰረተበት ቀን ሊመረጥ ችሏል።
ይህም ቀን ጥቅምት 15 /1900 ዓ/ም የአፄ ሚኒሊክ የጦር ሚኒስትር መ/ቤት ያቋቋሙበትና መስሪያ ቤቱን እንዲመሩ ሚኒስትር የሰየሙበት ቀን ነው።
ጥቅምት 15 /1900 ዓ/ም የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጦር ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ፊትአውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ / አባ መላ ነበሩ።
የዘንድሮው የሰራዊት ቀን ለምን በወታደራዊ ሰልፍ ትርኢት ለማክበር ተፈለገ ?
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራት ኃላፊ ሌ/ጄነራል ዓለምእሸት ደግፌ ዛሬ በመስቀል አደባባር በተካሄደው ዝግጅት ላይ ባሰሙት ንግግር " በዓሉ በወታደራዊ ሰልፍ ትርኢት እንዲከበረ የተፈለገው ለእይታ ስለሚማርክ ብቻ ሳይሆን ዋናው እሳቢያችን ዛሬም ነገም ሰላማችንን ለማወክ የሚመኙ ካሉ ሁሌም ዘወትር ዝግጁ መሆናችንን ከወዲሁ ለማሳሰብ ነው " ብለዋል።
በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የሰራዊት ቀን በዓል ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የጦር ሰራዊት አመራር እና አባላት፣ የክልል ባለስልጣናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው የአፍሪካ ሀገራት የጦር መሪዎች ...እና ሌሎችም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተው ነበር።
#ለጥንቃቄ
በ " ፌስቡክ " እንደልብ በሚተዋወቁ መልዕክቶች ምክንያት በርካታ ወጣቶች ውድ ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን እየተባሉ እየተጭበረበሩ ነው።
" ፌስቡክ " ላይ ግለሰቦች ክፍያ ከፈፀሙ " Sponsored " የሆኑ መልዕክቶችን ብዙ ሺህ ተጠቃሚዎች ጋር ያደርሳሉ።
ተቋሙ ገንዘብ እየተቀበለ የማያሰራጫቸውን መልዕክቶች ትክክለኝነት እያረጋገጠ ይሁን አይሆን የሚታወቅ አንዳች ነገር ባይኖርም በርካቶች ግን በሀሰተኛ መልዕክቶች ወጣቶች እየተጭበረበሩ ይገኛሉ።
ከሰሞኑን ስለ " ሀሰተኛ የትሬድ ስራ " እና በዛ ምክንያት ገንዘባቸው ተበልቶ እና መፍትሄ አጥተው ስለተቀመጡ ሰዎች ዳሰሳ መስራታችን ይታወሳል።
ለዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ መልክ ስለሚደረግ ማጭበርበር በአጭሩ እንመለከታለን፤ ይኸውም ዋና ዓላማቸው ስራ የሌላቸውን ወጣቶች እና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን በሀሰተኛ መልዕክቶች አታሎ ገንዘባቸውን ማጭበርበር ነው።
በፌስቡክ ላይ ስፖንሰር በሚሆን መልዕክት "
- ስራ የሌላችሁ ስራ እንቀጥራችኃለን፣
- በቀን ውስጥ ከ20 ሺህ ብር በላይ ትሰራላችሁ ፣
- በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ገንዘብ በማግኘት የራሳችሁን ስራ ትጀምራላችሁ " የሚሉ የማጭበርበሪያ መልዕክቶች በስፋት ሲሰራጩ ተመልክተናል።
ወጣቶች እነዚህን አካላት ለዚሁ ጉዳይ በሚያናግሯቸው ጊዜ በቅድሚያ የምዝገባ ገንዘብ ይጠይቋቸዋል፤ በኃላም የውሃ ሽታ ይሆናሉ።
የወጣቶችን ስራ ማጣት እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው ከሌላቸው ገንዘብ ላይ ለመንጠቅ የሚሰሩት እነዚህ አስነዋሪ አጭበርባሪዎች መልዕክታቸውን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀሙ ቢሆንም በይበልጥ የተከፈለባቸው የ " ፌስቡክ " መልዕክቶች ዋነኛዎቹ ናቸው።
ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ?
- አንድ የስራ ማስታወቂያ ስንመለከት ስራው የት እንደሆነ ? የቢሮው አድራሻ ? ህጋዊነቱን የሚያሳይ ማስረጃ ? መጠየቅ አለብን።
- " ስራ ለመቀጠር ብር ክፈሉ " የሚሉ ዘራፊዎችን ለምን ? ብሎ ማፋጠጥ ፤ እንዲሁም ስልካቸውን እና አድራሻቸውን መመዝገብ ይገባል።
- አንድ ስራ በቀን 100 ሺህ ፣ 50 ሺህ ብር ይከፈልበታል ሲባል እንዴት ? በምን መልኩ ? ምን ተሰርቶ ? በየትኛው ህጋዊ መንገድ ብሎ መጠየቅ እና መጠራጠር ይገባል።
በ " ፌስቡክ " ወይም በ " ቴሌግራም " ላይ የማረጋገጫ ምልክት ያላቸው ሰዎች ሁሉ እውነተኛ ናቸው ብላችሁ እንዳታምኑ፤ እነዚህ ምልክቱን ገዝተው መጠቀም ይችላሉና።
ከምን በላይ በተለይ " ፌስቡክ " በክፍያ የሚያስተላልፋቸውን መልዕክቶች ትክክለኝነትን የሚያረጋግጥበትን መንግድ መዘርጋት ካልቻለ ትልቅ ቀውስ መፍጠሩን ይቀጥላል።
ማንኛውም ሰው ተነስቶ ለፌስቡክ የመክፈያ መንገድ ካበጀ ፤ ዜሮ ተከታይ ቢኖረም ፤ ህገወጥ ዝርፊያ ላይ የተሰማራ ቢሆንም እስከከፈለ ድረስ ማስረጃ የሌለው መልዕክት ሊያሰራጭ ይችላል።
በተለይም በርካታ ወጣቶች ስራ ፈላጊ በመሆናቸው ስራ ያላቸው ዜጎችም ከሚያገኙት ገቢ የተሻለ ለማግኘት ሲሉ እነዚህን አካላት ያነጋግራሉ። የሚጠየቁትን ገንዘብም ክፈሉ ሲባሉ ሊከፍሉ ይችላሉ።
አንደንዶች ደግሞ በፌስቡክ የክፍያ መልዕክት የሌላቸው እና የማይሸጡትን ዕቃ በማስተዋወቅ ሰዎችን ገንዘብ ካስላኩ በኃላ የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ።
" ፌስቡክ " አሰራሩን ማስተካከል ካልቻለና ገንዘብ እየሰበሰበ ብቻ በትንሽ ዶላር ብዙሃን ጋር ያልተረጋገጡ መልዕክቶችን የሚያሰራጭ ከሆነ በተዘዋዋሪ ቁጥጥር ባለማድረጉ በተጠቃሚዎች ላይ ለሚደርሰው ድርጊት ኃላፊነት ሊውስድ ይገባል።
ከምንም በላይ ግን ተጠቃሚዎች እንዲሁም ውድ ቤተሰቦቻችን እራሳችሁን ከአጭበርባሪዎች ጠብቁ።
#Update
🔹 " የፌዴራሉ መንግሥት ያለንበትን ሁኔታ አይቶ መፍትሄ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፤ ... ጥያቄያችንን በወከልናቸው ሰዎች ለማቅረብም ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ዝግጅት እያደረግን ነው " - ነዋሪዎች
🔹" ሳንበላ ማከም አንችልም " - የጤና ባለሞያዎች
▪️ ባለስልጣናት ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ ሲደወልላቸው ስልክ አያነሱም አንዳንዶቹ ስልካቸው ዝግ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሃዲያ ዞን ፣ የምስረቅ ባድዋቾ ወረዳ ነዋሪዎች የህክምና እና የትምህርት አገልግሎት በመቋረጡ መቸገራቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን የሰራተኞች የወራት ደመወዝ ባለመከፈሉ የህክምና እና የትምህርት አገልግሎት ከተቋረጠ ቀናት ቢያልፉም እስከአሁን መፍትሄ እንዳልተገኘ ከነዋሪዎች ተሰምቷል።
የመንግሥት ሠራተኞች የጀመሩት የሥራ ማቆም አድማ ዛሬ ሰኞ ሁለተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረ ሲሆን ሠራተኞቹ የሥራ ማቆም አድማውን ማካሄድ የጀመሩት ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ያለው ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በመጠይቅ ነው።
ነዋሪዎቹ ምን አሉ ?
(በዶቼ ቨለ ሬድዮ)
- የወረዳው ሀኪሞችና መምህራን ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል ሥራ ካቆሙ ሁለት ሳምንት አስቆጥረዋል። በዚህ ምክንያት ልጆቻችን ቤት ለመዋል ተገደዋል፤ የታመሙ ሰዎችም ህክምና ለማግኘት ተቸግረዋል።
- በሠራተኞቹ አድማ የተነሳ በወረዳው የሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት አሁን ድረስ አገልግሎታቸው እንደተስተጓጎለ ነው።
- የሾኔ ሆስፒታልን ጨምሮ የህክምና ተቋማትና ትምህርትት ቤቶች ሙሉ በሙሉ በመዘጋታቸው ለከፍተኛ ችግር ተደራገናል።
- በሠራተኞች ደሞዝ አለመከፍል ምክንያት የተቋረጡ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማስቀጠል በአካባቢው ባለሥልጣናት በኩል የሚደረግ ጥረት የለም።
- ችግሩ ከወረዳ፣ ከዞኑና ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ ይመስላል። የፌዴራሉ መንግሥት ያለንበትን ሁኔታ አይቶ መፍትሄ እንዲሰጠን እንፈልጋለን። ጥያቄያችንን ለማቅረብም በወከልናቸው ሰዎች አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ዝግጅት እያደረግን ነው።
የመንግሥት ባለልስጣናት ምን ምላሽ ሰጡ ?
ሬድዮ ጣቢያው የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ አስተዳደር፣ የሃድያ ዞን የሰው ሀብት ልማትና የመንግሥት አገልግሎት መምሪያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት ቢያሰርግም ባለሥልጣናቱ " ስብሰባ ላይ ስለሆንን ቆይታችሁ ደውሉ " የሚል ምላሽ ከሰጡ በኃላ በተባለው ሰዓት ሲደወልላቸው አንዳንዶች ጭራሽ ጥሪ አይመልሱም፤ የተቀሩት ደግሞ ሥልካቸው ተዘግቷል።
በሌላ በኩል ፤ የአካባቢው ባለሥልጣናት ትናንት እሑድ የሾኔ ሆስፒታል ሠራተኞችን ያነጋገሩ ቢሆንም ከስምምነት ሳይደርሱ መቅረታቸውን አንድ የሆስፒታሉ ሠራተኛ አሳውቀዋል።
ሠራተኛው ስብሰባውን ለጠሩት የወረዳው አመራሮች " ሳንበላ ማከም አንችልም " የሚል ምላሽ መሰጠቱን የጠቀሱት እኝሁ አስተያየት ሰጪ " መጀመሪያ ደሞዛችንን አስገቡልንና ወደ ሥራ እንመለሳለን የሚል ምላሽ ከሠራተኛው በኩል ተነስቷል ፤ መፍትሄው መክፈል ብቻ ነው ከዚህ ውጭ አማራጭ የለም በሚል ከአመራሮቹ ጋር ከስምምነት ሳንደርስ ቀርተናል " ብለዋል።
ቁጥራቸው ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት በሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ መንግሥት ሠራተኞች " የሠራንበት የሦስት ወር ደሞዝ ይከፈልን " በሚል ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ በሥራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው።
ለሠራተኞቹ ደሞዝ መክፈል ያልተቻለው የቀድሞው የደቡብ ክልል ለወሰደው የአፈር ማዳበሪያ ብድር የወረዳውን ባጀት በዋስትና በማስያዙ እንደሆነ ከዚህ በፊት የወረዳው ባለሥልጣናት መግለፃቸውን ዶቼ ቨለ ሬድዮ በዘገባው አስታውሷል።
Credit - #DeutscheWelleRadio
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ፦
" ... በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቀማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት በህጉ አግባብ ብቻ መከናወን ይኖርበታል። ይህ አለመሆኑ ግን ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገፅታ ላይ ጥላ የሚያጠላ ሆኗል፡፡
ላለፉት አምስት ዓመታት የፍትህ አካሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ያለ ቢሆንም ጋዜጠኞችንና ተቋማቱን በተመለከተ በሕጉ አግባብ ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ያለመቻሉ ምክር ቤታችንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡
ችግሩ እንዲፈታም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ጉዳዩን በማሳወቅ ክትትል እያደረገ ነው፡፡ "
(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)
" ያፈራሀው ሃብት ውጤት የሚኖረው ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ በሚችል ቁምነገር ስታውለው ነው " - ባለሃብቱ ዘርኡ ገ/ሊባኖስ
ባለሃብቱ በሰባቱ የትግራይ ዞኖች ሰባት ትምህርት ቤቶች ለመገንባት የሚያስችል የሰምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።
ትምህርት ቤቶቹ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የመነሻ ካፒታል ናቸው የሚገነቡት።
ባለሃብቱ ኣቶ ዘርኡ ገ/ሊባኖስ ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም በመቐለ በተከናወነው የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥና የስምምነት ፊርማ ስነ-ሰርአት እንዳሉት ፤ " ያፈራሀው ሃብት ውጤት የሚኖረው ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ በሚችል ቁምነገር ስታውለው ነው " ብለዋል።
ትግራይ በደም አፋሳሹ ጦርነት ምክንያት ያጋጠማት ውድመት ከፍተኛ መሆኑ የጠቆሙት ባለሃብቱ ፤ ሁሉም በየአቅሙ በመልሶ ግንባታ በመሳተፍ ለትውልድ የሚተርፍ ቅዱስ ነገር መፈፀም እንዳለበት አሳስበዋል።
በማብሰሪያ ስነ-ሰርዓቱ የተገኙት የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ፤ " በጦርነት የወደመቸው ትግራይ መልሶ ለመገንባትና የተሰው ታጋዮች አደራ ለመፈፀም በሚደረገው ጥረት የሁሉም ትግራዋይ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ነው " ብለዋል።
በስነ-ሰርዓቱ ማብሰሪያ እንደተገለፀው የሚገነቡት ሰባት ትምህርት ቤቶች ለያንዳንዳቸው ብር 50 ሚሊዮን ፤ በአጠቃላይ 350 ሚሊዮን ብር መመደቡንና በጥራትና በጊዜ ሰሌዳ ለመፈፀም ይሰራል ተብሏል።
ባለሃብቱ አቶ ዘርኡ ገ/ሊባኖስ የተቸገሩትን በመርዳት ባሳዩት መልካምነት ከናይጀሪያው ዎልደስ የኒቨርስቲ መስከረም 9/2016 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል።