#Update
" በሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ " ላይ የመጨረሻ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ረቂቁ ከባለፈው መጠነኛ #ማሻሻያዎች ተደርጎበት መቅረቡን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።
ምንድናቸው ?
በመጀመሪያው ረቂቅ አዋጅ ያልነበረና የመንግሥትንና የክልሎችን ግዴታና ኃላፊነት በመዘርዘር የተቀመጠው ክፍል አንዱ ነው።
በዚህ ክፍል ላይ መንግሥት በሃይማኖት አስተምህሮና የውስጥ ጉዳይ #ጣልቃ_መግባት_እንደማይችል ተደንግጓል፡፡
በተጨማሪ ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ከውጭ አገር የሚላክለትን የገንዘብ ዕርዳታ፣ ስጦታ ወይም ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችን በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ እንደሚኖርበት ተደንግጎ የነበረው የረቂቅ አዋጁ ክፍል ከተሻሻለው ረቂቅ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
ነገር ግን ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ፦
° የሃይማኖት ተቋሙን ኦዲት ሪፖርት ለሰላም ሚኒስቴር እንዲያቀርብ፣
° የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ #በ3_ወራት የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በገለልተኛ ኦዲተር ማስመርመር እንደሚኖርበት የተቀመጠው የረቂቁ ክፍል በተሻሻለው ላይ #ተካቷል፡፡
ሌላኛው ተሻሽሎ የቀረበው የረቂቅ ክፍል #አለባበስን እና የተማሪዎች #አመጋገብን ጨምሮ በማንኛውም የትምህርት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚደረግ ሃይማኖታዊ ተግባር የመንግሥትና ሃይማኖት መለያየት መርህንና የሃይማኖት ነፃነትንም በጠበቀ መንገድ መከናወን አለበት የሚለው ነው፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ምን አሉ ?
የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ #የመጨረሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም #በመንግሥት እና #በሃይማኖት መካከል ያለው ልዩነት ምን ድረስ እንደሆነ ሳይታወቅ ቆይቷል ብለዋል።
አዋጁን ማዘጋጀትም ያስፈለገው ይህን ጉዳይ በግልጽ ለማስቀመጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መንግሥት በሃይማኖት ተቋማት ነፃነት ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ፤ ነገር ግን አብረው በሚሠሩባቸው ጉዳዮች በሕግ የተቀመጠ አሠራር ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተነሱ ሐሳቦችን በግብዓትነት #ወስዶ ለሚመለከተው አካል የሚቀርበውን ረቂቅ አዋጅ እንደሚያዘጋጅ ተገልጿል፡፡
Credit - Reporter Newspaper
#WKU
" አንድ ተመራቂ ተማሪ እና አንድ መምህር ጉዳት ካስተናገዱ በኋላ ሁኔታዉ በቁጥጥር ስር ውሏል " - የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አመራር
ከሰሞኑ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አንድ ሽጉጥ የታጠቀ ወጣት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተኩስ በመክፈቱ አንዲት ተመራቂ ወጣት እና አንድ መምህር ተጎድተዋል።
የግቢዉ ተማሪዎች bbc ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በወቅቱ የተፈጠረው የተኩስ ድምጽ እና ሁኔታ እጅግ ረብሿቸው ነበር።
ይሁንና " ታጥቆ ወደ ግቢው የገባው አካል በቁጥጥር ስር መዋሉና ሰላም መሆኑ " ተነግሯቸው ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስረድተዋል።
ሁኔታውን በተመለከተ አስተያየታቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊ " ጉዳዩ ድንገት በመፈጠሩ ለጥቂት ሰአታት ግርግር ቢፈጥርም በግቢዉ የጸጥታ ሀይል በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል " ብለዋል።
በወቅቱ " የመመረቂያ ጽሁፍን በዲስፕሊን ምክኒያት እንዳያቀርብ የተከለከለ የነርሲንግ ተማሪ ሽጉጥ ታጥቆ በመምጣት ጉዳት አድርሷል " ሲሉ ገልጸዋል።
" የመመረቂያ ወረቀቷን ታቀርብ የነበረዉንና ጓደኛዬ የሚላትን ' እኔ ካላቀረብኩ አንችም አታቀርቢም ' በማለት ሽጉጥ ተኩሶ በማቁሰል በዛ የነበሩትን መምህራን አባሯል " ሲሉ አስረድቷል።
ከዚህ በኋላ ሰዎችን ባይጎዳም ደጋግሞ መተኮሱ በግቢው ውስጥ ችግር መፍጠሩን የሚገልጹት ሀላፊዉ ይህም ተማሪዎችን መረበሹን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት የተሰማዉን የተኩስ ድምጽ የሰማዉ የግቢዉ የጸጥታ ሀይል ወጣቱን በፍጥነት በመቆጣጠር ሁለቱን ተጎጅዎች ወደህክምና ሊወስዳቸዉ እንደቻለና ገልጸዋል።
በወቅቱ ከተከሰተዉ ችግር ለመሸሽ መምህራኑ ባደረጉት ጥረት አንዱ በመስኮት ሲዘል ከፍተኛ አደጋ እንደደረሰበትና የሁለት እግሮቹ አጥንቶች ተሰብረዉ ከፍተኛ የአጥንት ህክምና በማስፈለጉ የግቢዉ ማህበረሰብ ገንዘብ እያወጣለት መሆኑን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለማወቅ ችሏል።
አንድ ጉዳዩን የምታውቅ ተማሪ ፤ " 1 ወር ከ15 ቀን ልጅ በፊት ደብድቧት ሆስፒታል ገብታ ፤ እሱም 2 ዓመት ተቀጥቶ ነበር። ከዛም በፊት መትቷት ያቃል። ባለፈው ደግሞ ዲፌንስ አቀርባለው ብሎ ሲከለከል ሽጉጥ ይዞ መተኮስ ጀመረ ልጅቷን ተኩሶ ስቷቷል ፤ ከዛ ይዞ ደብድቧታል። ጭንቅላቷ ተፈንክቷል። አንድ መምህርም ከፎቅ ዘሎ ተሰብሯል። አንድ ተማሪም ወድቃ ጭንቅላቷ ውስጥ ደም ፈሶ ሰርጀሪ ተሰርቶላታል " ብላለች።
#Attention ⚠️
" ራኒቲዲን #ካንሰርን ሊያመጣ የሚችል ንጥረ ነገር በውስጡ በመገኘቱ ምክንያት #ታግዷል የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን
ለጨጓራ ተያያዥ ህመሞች በመድኃኒትነት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ' ራኒቲዲን ' የተባለው መድሃኒት በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል #ማገዱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አሳውቋል።
የባለስልጣኑ የመድኃኒት ደህንነት ክትትልና የሕክምና ሙከራ መሪ ስራ አስፈጻሚ አስናቀች ዓለሙ ፤ " በመጀመሪያ ደረጃ በሌሎች ሀገር የወጡ ሪፖርቶችን አይተን ነበር። ስለዚህ በሀገራችንስ ይሄ መድሃኒት እንዴት ነው ? የሚለውን በማገናዘብ የላብራቶሪ ምርመራ አድርገናል " ብለዋል።
በዚህም መድሃኒቱ ካንሰር ሊያመጣ የሚችል ' N-nitrosodimethylamine ወይም NDMA ' የተሰኘ ንጥረ ነገር እንደተገኘበት መሪ ስራ አስፈፃሚዋ ገልፀዋል።
" በመሆኑም ይህንን መድሃኒት ከምዝገባ ፋይላችን አውጥተናል። የተሰራጩ መድሃኒቶችም #እንዲሰበሰቡ እና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መልእክት አስተላልፈናል " ብለዋል።
" በዚህ በሰረትም ጥቅም እንዳይውል #ታግዷል " ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።
" የጤና ባለሙያዎችም፣ የጤና ተቋማትም ሌሎች አማራጭ መድሃኒቶችን እንዲያዙ እና እንዲጠቀሙ ይህንን መድሃኒት #እንዳይጠቀሙ " ሲሉም አሳስበዋል።
#መቐለ
ከሳምንት በፊት " በአፈልጉን ማስታወቅያ " ስትፈለግ የሰነበተች ተማሪ በውሃ ጉድጓድ ውስጥ ሞታ ተገኘች።
ተማሪ ቤቴልሄም ገብረሚካኤል ነጋሽ ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ/ም ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ላይ ነው በመቐለ ከተማ ፤ ዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ዓዲ ሓውሲ ቀበሌ ከሚገኝ ቤትዋ እንደወጣች የቀረችው።
ዛሬ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ/ም ግን አስክሬኗ ደብሪ ቀበሌ ጨለዓንቋ ተብሎ በሚታወቅ ኩሬ ተጥሎ መገኘቱ ተገልጿል።
የ17 ዓመትዋ ተማሪ ቤቴልሄም በመቐለ የቀላሚኖ ልዩ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረች ስትሆን ከአንድ ሳምንት የአፋልጉን ጥሪ በኋላ በውሃ ጉድጓድ አስክሬኗ ተጥሎ መገኘቱ ብዙዎችን አስደንግጧል፤ አሳስዝኗል።
የተማሪዋ አስክሬን በፓሊስ ትእዛዝ ወደ ዓይደር ሪፈራል ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል ተወስዶ ከተመረመረ በኋላ አመሻሽ በመቐለ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስትያን በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።
በቀብር ስነሰርዓቱ ላይ ቤተሰቦች፣ የቀላሚኖ ትምህርት ቤት ኮሙዩኒቲ ፣ ወዳጆች እና አብሮ አደጎችን ጨምሮ በርካታ ህዝብ በመገኘት የተሰማው ጥልቅ ሃዘን በእንባ በመታጀብ ገልጿል።
በቀብር ስርዓቱ ላይ የተገኘው ህዝብ ፍትህ ጠይቋል።
የአሟሟትዋ ጉዳይ እጅግ በጣም ያሳዘናቸው የተለያዩ የህብረተሰብ አካላት ወንጀሉ ተጣርቶ ወንጀለኞች ወደ ህግ እንደዲቀርቡ ጠይቀዋል።
ፖሊስ በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ ካለ ተከታትሎ እንደሚልክ የመቐለው ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ገልጿል።
#ኢትዮጵያ
በሀገሪቱ ውስጥ ያለ ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርቱን ለሰላም ሚኒስቴር ማቅረብ እንደሚኖርበት ፤ ከውጭ አገር የሚመጣ የገንዘብ ዕርዳታ በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ እንደሚኖርበት የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።
" የሃይማኖት ጉዳዮች አዋጅ " የተሰኘው ረቂቅ አዋጁ የሃይማኖት ተቋማቱ ተቀባይነት ያለው የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚኖርባቸው፣ የኦዲት ሪፖርታቸውን ለሰላም ሚኒስቴር ማቀረብ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ምን ይዟል ?
- የሃይማኖት ተቋማት የሚጠቀሙት የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት የገቢ፣ የወጪና አጠቃላይ የንብረት ዝርዝር የያዘ መሆን አለበት።
- የገቢ አሰባሰብና የወጪ አስተዳደር በሕጋዊ መንገድ ማከናወን አለባቸው።
- የሃይማኖት ተቋም በራሱ #የገቢ_ማስገኛ ሥራዎችን በሚያከናውንበት ጊዜ ለዚሁ ሥራ ሲባል የተለየ የባንክ ሒሳብ መክፈትና የተለየ መዝገብ መያዝ አለበት።
- ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ከውጭ የሚላክለትን የገንዘብ ዕርዳታ፣ ስጦታ ወይም ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችን በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ አለበት። ሲያሳውቅም ፦
° የለጋሹን ድርጅት ወይም ግለሰብ ስም እና አድራሻ፣
° የተለገሰው የገንዘብ፣ ስጦታ ዓይነት እና መጠን ፣
° ስጦታው / ድጋፉ የተሰጠበት ልዩ ዓላማ መካተት አለበት።
- ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የበጀት ዓመቱ ባለቀ በ3 ወር ውስጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በገለልተኛ ኦዲተር ማስመርመር አለበት። የኦዲተሩን አቋም እና የውሳኔ ሐሳብም መያዝ ይኖርበታል።
- የሰላም ሚኒስቴር የደረሰውን የኦዲት ሪፖርት አመቺ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርበታል።
#ሪፖርተርጋዜጣ
#USA #kenya
የጎረቤታችን ሀገር ኬንያን ፕሬዜዳንት ዊሊያም ሩቶን ተቀብለው እያስተናገዱ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኬንያን ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል የመጀመሪያዋ #የNATO_አባል_ያልሆነች (non-NATO) ዋና አጋር ሀገር እንደምታደርጋት ቃል መግባታቸው ተነግሯል።
#ጥቆማ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር /INSA / የ " ብሄራዊ የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ፕሮግራም - National Cyber Talent Challenge Program " ማዘጋጀቱን ገልጿል።
በሳይበር ደህንነትና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ እና ፍላጎት ያላቸው በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሙሉ በዚህ ቻሌንጅ ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጿል።
የታለንት መስኮች፦
- Cyber Security
- Cyber Development
- Embedded Systems
- Aerospace ናቸው።
ስልጠናው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ለአንድ ወር ይሰጣል።
አመልካቾች በዌብሳይት https://talent.Insa.gov.et በመግባት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 30/ 2016 ዓ/ም መመዝገብ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ለበለጠ መረጃ ደግሞ በ +251910974317 ወይም +251904311837 ላይ ስልክ መደወል ይቻላል።
#OnlineNationalExam
ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና መንግሥት በሚያዘጋጃቸው ኮምፒውተሮች እንደሚከናወን የሀገር አቀፍ ትምህርት፣ ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ለኢቢሲ ገልጿል።
አንዳንድ ወላጆች " በኦንላይን ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና የመፈተኛ ኮምፒውተር እንድናቀርብ ተጠይቀናል " ብለዋል።
አገልግሎቱ ግን ይህንን በሚመለከት ለትምህርት ቤቶች ያስተላለፈው መልዕክት እንደሌለ እና ወላጆች መጠየቃቸውም ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።
የኦንላይን ፈተናው መንግስት በሚያዘጋጀው አቅርቦት እንደሚከናወን አመልክቷል።
ተማሪዎች ለፈተና ሲመጡ የሚጠበቅባቸው አንብቦ እና በቂ ዝግጅት አድርጎ የተመዘገቡበትን መታወቂያ ይዞ መምጣት ብቻ ነው ብሏል።
ነገር ግን ትምህርት ቤቶችም ሆኑ ተማሪዎች የግል ኮምፒውተሮቻቸውን ለፈተናው መጠቀም ከፈለጉ #እንደማይከለከሉ አገልግሎቱ አሳውቋል።
ሁሉም ተማሪዎች በኦንላይ እንዳይፈተኑ የመሰረተ ልማት አለመሟላት እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል ዘንድሮ #በተወሰኑ ተማሪዎች ብቻ እንደሚጀመር ገልጿል።
በሌላ በኩል ፥ በወረቀት ለሚሰጠው ፈተና የህትመት ስራው ወደ #መጠናቀቅ መቃረቡን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ለኢቢሲ በሰጠው ቃል አመልክቷል።
ይህ እንዴት ይታያል ?
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በኦንላይን ለሚሰጠው ፈተና " ትምህርት ቤቶች ሆኑ ተማሪዎች #የግል_ኮምፒዩተራቸውን ለፈተና መጠቀም አይከለከሉም " ብሏል።
ተማሪዎች የራሳቸውን ኮፒዩተሮች ይዘው ሲገቡ በውስጡ ለፈተና ደህንነት የሚያሰጋ ወይም ፈተናውን እንዲሰሩ የሚያግዛቸው የተለያየ ዶክመት ተደብቆበት እንዳልሆነ የሚረጋገጥበት ምን አይነት መንገድ እንዳለ አልተብራራም።
ሌላው ተፈታኞች በፈተና ወቅት በኢንተርኔት ድረ ገጾችን በመጎብኘት ጥያቄ የሚሰሩበት መንገድ እንዳይኖር ስለሚወሰደው የጥንቃቄ እርምጃ የተብራራ ነገር የለም።
መሰልና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ችግር ይዘው እንዳይመጡ ከወዲሁ ማሰብና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
ሁሉንም የግንባታ ባለሙያዎች እየጠራን ነው።
በቢግ ፋይቭ ኮንስትራክት ኢትዮጵያ 2016 ለይ የሚሳተፉ ከ150 በላይ የግንባታው ዘርፍ ብራንዶችን ይተዋወቁ።
ዩናይትድ አረብ ኢምሬት፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ኢትዮጵያ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ህንድ፣ ቱርክና ኦስትሪያን ጨምሮ ከተለያዩ 20 ሃገራት ተወክለው ከሚመጡ ተሳታፊዎች(አቅራቢዎች) ጋር ይገናኙ።
የአቅራቢ ድርጅቶችን ዝርዝር ይመልከቱ፦ https://bit.ly/44BfWyw
ይህ በዘርፉ መልካም ስም ካተረፉ ድርጅቶች ጋር የመገናኘት አስደሳች አጋጣሚ አያምልጥዎ!
በነጻ ለመግባት እዚህ ይመዝገቡ https://bit.ly/3UsrL5I
በቢግ ፋይቭ ኮንስትራክት ኢትዮጵያ
ትምህርት ሚኒስቴር የመውጫ ፈተና ድጋሚ ተፈታኞች የምዝገባ ጊዜን አሳወቀ።
በ2016 ዓ/ም ሰኔ ወር ላይ የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና በድጋሚ ለመውሰድ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ተፈታኞች ምዝገባ የሚከናወነው ከግንቦት 14 እስከ 21/2016 መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል።
የምዝገባ ክፍያ 500.00 ብር በመክፈል በ https://exam.ethernet.edu.et በኩል መመዝገብ ይችላሉ ተብሏል።
የአገልግሎት ክፍያ 500.00 ብር በ ' ቴሌ ብር ' ብቻ የሚፈጸም መሆኑ አስገንዝቧል።
#ለመጀመሪያ_ጊዜ የመውጫ ፈተና የሚፈተኑ እጩ ተመራቂዎች ምዝገባ የሚካሄደው እና የአገልግሎት ክፍያ በተቋማቸው በኩል መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ አስፈላጊ የመፈተኛ መረጃዎችን በተቋማቸው በኩል እንደሚደርሳቸው አሳውቋል።
በሀዋሳ ከተማ የስፓርት ውርርድ #ቤቲንግ ቤቶች እየታሸጉ ይገኛሉ።
ይህ ተከትሎ የስፖርት ውርርድ ቤት ባለቤቶች " እንዴት የንግድ ፈቃድ እያለን ይዘጋብናል ? ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
እነዚህ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ከወራት በፊት በተለያዩ ምክኒያቶች ተዘግተው የቆዩ ሲሆን በቅርቡ ተከፍተው ነበር።
አሁን ላይ ተመልሰው መዘጋት መጀመራቸው ግራ እንዳጋባቸውና ልክ እንደባለፈዉ ጊዜ ከስራቸዉ ተስተጓጉለው ቤት መዋል መጀመራቸው እንዳሳዘናቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ
° ቤቶቹን ለምን ታሸጉ ?
° መፍትሄውስ ምንድን ነው ? ሲል የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር ጠይቋል።
እሳቸውም #በሲዳማ_ክልል_ስር የወጣ አንድም የንግድ ፈቃድ የለም ብለዋል።
" ከወራት በፊት ከነዚህ አካላት ቤቲንግ ቤቶች ጋር በነበረን ውይይት የንግድ ፈቃድ በማውጣት ህጋዊ እንዲሆኑ ተግባብተን ነበር " ሲሉ አስታውሰዋል።
" ይሁንና ከረዥም ጊዜ በኋላ ዳግም ስናጣራ አሁንም ህጋዊ መሆን አልቻሉም " ያሉት ሀላፊው " ከዚህ ባለፈም እነዚህ ቤቶች በትምህርት ቤት ፣ በሀይማኖት ተቋማትና በመኖሪያ ሰፈሮች እንዲሰሩ አይፈቀድም ሌላዉ የመዘጋታቸዉ ምክኒያት ይኸው ነው " ሲሉ አሳውቀዋል።
ለግለሰቦቹ በሰላማዊ መንገድ ምክንያቱ ተነግሯቸው ቤታቸዉ እየተዘጋ መሆኑን የገለጹት አዛዡ ፤ " ከዚህ ዉጭ ' ገንዘብ ተወሰደብኝ ' እንዲሁም ' የአላግባብ ህገወጥ የሆነ ተግባር ተፈጽሞብኛል ' የሚል አካል በማንኛዉም ሰአት ወደ ሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመምጣት ሊያመለክት ይችላል ብለዋል።
ቤቶቹ ተመልሰው #የመከፈት እድል አላቸዉ ወይ ተብለው የተጠየቁት ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ " መጀመሪያ ህጋዊ ይሁኑ ከዛ በኋላ ከፖሊስ በተጨማሪ የሚመለከታቸዉ አካላት የሚመለከቱት ጉዳይ ይሆናል " ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።
#ኢራን
" ...አሜሪካ በአቪየሽን ዘርፍ ላይ የጣለችው ማዕቀብ ለአደጋው መንስዔ ነው " - ሙሐመድ ጃቫር ዛሪፍ
የኢራን የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሃመድ ጃቫር ዛሪፍ ፣ የኢራን ፕሬዝዳንት እና ሌሎች ከፍተኛ የኢራን ባለስልጣናት ላይ ለደረሰው የሄሊኮፕተር አደጋ አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።
ሙሃመድ ጃቫር ዛሪፍ ፣ " #አሜሪካ በአቪየሽን ዘርፍ የጣለችው ማዕቀብ ለአደጋው መንስዔ ነው " ብለዋል፡፡
ከኢራን ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ደረጉት ዛሪፍ ፣ " ማዕቀቡ ኢራን #አዳዲስ የአቪየሽን ምርቶችን መግዛት እንዳትችል አድርጓታል " ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢራን ከአሜሪካ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንደሌላት ይታወቃል።
ትላንት የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ እና ሌሎች ባለልስጣናት ግድቦችን መርቀው ከከፈቱ በኋላ ወደ ታብሪዝ እያመሩ ሳሉ የነበሩበት ሂሊኮፕተር ከተራራ ጋር ተጋጭቶ ሁሉም ህይወታቸው አልፏል።
አደጋው በደረሰበት አካባቢ ላይ እጅግ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ እንደነበርም ተገልጿል።
#Ethiopia
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢንጂነር አይሻ መሀመድ እና ዶ/ር አብርሃም በላይን የስልጣን ቦታ ቀያየሩ።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ሰጥተዋል።
በዚህም ፦
1. ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚንስትር ፣
2. ዶ/ር አብረሃም በላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሚንስትር ፣
3. ዶ/ር መሀመድ እንድሪስ ደግሞ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አድርገው ሾመዋቸዋል።
ኢ/ር አይሻ መሀመድ በ2011 ዓ/ም የመጀመሪያዋ ሴት የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኃላ 6 ወር እንዳገለገሉ ከቦታው ተነስተዋል።
ዶ/ር አብርሃም በ2014 ነበር የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት።
ዶ/ር አብርሃም በላይ የአሁኑ ሹመት እስኪሰጥ ድረስ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት እያገለገሉ የነበሩ ሲሆን አሁን በኢ/ር አይሻ መሀመድ ተተክተው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነዋል።
#StockMarket
(የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን በቅርበት በሚከታተሉት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በአንድ ወቅት ለቢቢሲ ድረገፅ ከሰጡት ቃለምልልስ የተወሰደ)
ስቶክ ገበያ ምንድነው ?
ለስቶክ ማርኬት ‘ የድርሻ ገበያ ’ የሚል አቻ የአማርኛ ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን።
ኩባንያዎች የኩባንያውን የባለቤትነት ድርሻ ለገበያ ያቀርባሉ።
ሰዎች ይህን ድርሻ ከገዙ በኋላ ኩባንያው ትርፋማ በሆነ መጠን ያላቸውን ድርሻ መልሰው በመሸጥ ወይም ከትርፍ ክፍፍል ትርፋማ የሚያደርግ አሠራር ነው።
ስቶክ ማርኬት ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል ?
የስቶክ ገበያ በዋናነኝነት ለኢትዮጵያ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይዞ ይመጣል።
1. የካፒታል ገበያ
በርካታ የአገር ውስጥ ባንክ እንዲሁም ኢንሹራንሶች ሲመሠረቱ እና ከምሥረታቸውም በኋላ የአክሲዮን ድርሻዎችን ሲሸጡ ቆይረዋል።
የስቶክ ገበያን ከዚህ የተለየ የሚያደርገው ፤ ይፋዊ በሆነ መልኩ ተደራጅቶ ቁጥጥር እየተገደረገበት በግልጽ መገበያየት ማስቻሉ ነው።
የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ እውን ሲሆን ፤ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ሲቋቋሙም ሆነ ማስፋፋት ሲፈልጉ አክሲዮን ለመሸጥ ይከተሉት የነበረውን ረዥም መንገድ ያሳጥርላቸዋል።
እነዚህ ኩባንያዎች ሲቋቋሙ ስቶክ ኤክስቼንጅ ስላልነበረ በጣም ረዥም ሂደት በማለፍ ለእያንዳንዱ ሰው እየዞሩ ነው ሼር የሚሸጡት።
ይህ ረዥም ጊዜ እና ገንዘብ ይወስዳል። አዋጭም አይደለም።
የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ አንዱ ጥቅም አዲስ ለመሚሠረቱም ሆነ ለነባር ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን መፍጠሩ ነው።
ካፒታል ማሰባሰብ ለሚፈልጉ ስቶክ ገበያ መልካም አማራጭ ነው።
ጥሩ ሐሳብ ኖሯቸው የካፒታል እጥረት ላለባቸው ሰዎች ይጠቅማል።
ዛሬ ላይ ከባንክ ብድር ማግኘትም ቀላል አይለደም። ለዘመድ ወይም ለጓደኛ ሼር የመሸጥ ሂደት ቀላል አይደለም። ስቶክ ማርኬት አዲስ ለሆኑም ይሁን መስፋፋት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን ይፈጥራል።
2. ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል
የስቶክ ገበያ ፣ ፍትሐዊ እና ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ ሀብት ማከፋፈል የሚችል ሥርዓት ነው።
በአሁኑ ጊዜ ግዙፍ መንግሥታዊ ኩባንያዎች ወደ ግሉ ዘርፍ እየተሸጋገሩ ነው።
እነዚህ ከመንግሥት ወደ ግሉ የሚዘዋወሩት ግዙፍ ኩባንያዎችን ሲገዙ የቆዩት ጥቂት ግለሰቦች እና ኮርፖሬሽኖች ናቸው። ስቶክ ማርኬት ሲመጣ ግን መንግሥት የሕዝብን ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል ይችላል።
ስቶክ ማርኬት ላይ 1 ሼር በአምስትም፣ በአሥርም ዶላር ሲሸጥ ሁሉም የየአቅሙን በመግዛት ኢትዮጵያ ያካበተችውን ሀብት ማከፋፈል ይቻላል።
እነዚህ ወደ ግሉ ዘርፍ የሚዘዋወሩ ኩባንያዎች ወደ ስቶክ ገበያው ሲገቡ፣ ሁሉም የአቅሙን ያህል ባለቤት ይሆናል። ይህም የሀብት ክፍፍልን ያመጣል።
3. ቁጠባ እና የኢንቨስትመንት አማራጭን ማስፋት
የቁጠባ ባህልን ከፍ ያደርጋል። ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ኪሳራ አያስከትልም ብለው በሚያስቡት ዘርፍ ላይ ብቻ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ።
ገንዘብ ያላቸው ሰዎች #የቤቶች_ልማት ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርጉ ይታያል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ደግሞ ተጎድቷል። ይህም ኢንቨስት የሚደረግባቸው ዘርፎችን ውስን በማድረግ የቁጠባ አለመመጣጠን ይፈጥራል።
ስቶክ ማርኬቱ ግን ውጤታማ በሆነ መንገድ ካፒታል በሁሉም ዘርፎች ላይ ማሰራጨት ያስችላል።
4. ግልጽነት
የድርሻ ገበያዎችን በቀላሉ፣ ግልጸኝነት በሰፈነበት መልኩ መግዛት እና መሸጥ ማስቻሉ ነው።
ምን ያህል ሼር በምን ያህል ዋጋ ለገበያ እንደቀረበ ግልጽ ነው።
ሰዎች ስልካቸው ላይ በሚጭኑት መተግበሪያ በቀላሉ የገበያ ድርሻዎችን መግዛት እና የገዙትንም መሸጥ ይችላሉ።
የባንክ ባለ አክሲዮኖች ዓመት ጠብቀው ትርፍ ከመከፋፈል ውጪ በቀላሉ ያላቸውን አክሲዮን መሸጥ አይቻላቸውም።
ስቶክ ማርኬት ሲሆን በቀላሉ አክሲዮን የመሸጥ ዕድል ይዘረጋል።
በስቶክ ገበያ ትርፍና ኪሳራ እንዴት ያጋጥማል ?
ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስቶክ ገበያ ምንድን ነው ? እንዴትስ መሸጥ እና መለወጥ ይቻላል ? የሚለውን እንመልከት።
ስቶክ ገበያን በቀላል ቋንቋ ለመረዳት የምጣሄ ሀብት ባለሙያዎች አዘወትረው የሚጠቀሙትን ቀላል ምሳሌ እንውሰድ። 'ሀ'፣ 'ለ' እና 'ሐ' የሚባሉ ሦስት ምናባዊ የሞባይል ስልክ አምራች ኩባንያዎችን አሉ አንበል።
እርስዎ 6 ዶላር አውጥተው ከእያንዳንዱ ኩባንያ የሁለት ዶላር የገበያ ድርሻ ይገዛሉ።
'ሀ' ለገበያ ያቀረበው ሞባይል ስልክ ባትሪ እየፈነዳ ሰዎችን ለጉዳት እየዳረገ መሆኑን የሚያመለክት ሪፖርት መውጣት ይጀምራል።
የ'ለ' ኩባንያ የሆነው ምርት ደግሞ ባትሪ በፍጥነት እያለቀ ከተጠቃሚዎች ቅሬታ ይደርሰዋል።
የ'ሐ' ምርት የሆነው ሞባይል ስልክ ግን በአግባቡ ይሠራል።
ይህ በገበያ ላይ ያጋጠመው ክስተት በሦስቱ ኩባንያዎች ስቶክ ገበያ ዋጋ ላይ ለውጥ ያመጣል። የአንድ ኩባንያ ምርት ጥራት ሲወርድ የዚያ ኩባንያ ፈላጊዎች ይቀንሳሉ።
በተቀራኒው አንድ ኩባንያ ትርፍማ የሚያደርገውን ውሳኔ ወስኖ ትርፍ ሲያጋብስ፣ የትርፉ ተቋዳሽ መሆን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከፍ ይላል።
በዚህ መሠረት ባትሪው እየፈነዳ ሰዎችን ለአደጋ እያጋለጠ ያለው የሞባይል ኩባንያ ድርሻ በከፍተኛ መጠን ሊወርድ ይችላል።
በሁለት ዶላር የገዙትን ድርሻ መልሰው መሸጥ ቢፈልጉ ከግማሸ ባነሰ ዋጋ እንኳን የሚገዛዎትን ላያገኙ ይችላሉ።
ይህ ሞባይል አምራች ኩባንያ ሲከስር እርስዎም የኩባንያው ባለድርሻ እንደመሆንዎ ኪሳራ ያጋጥምዎታል።
ስለዚህ በኩባንያ 'ሀ' ላይ ያደረጉት ኢንቨስትመንት ኪሳራን ያስከትላል።
የ 'ሐ' ምርት የሆነው ስልክ ግን በገበያ ተፈላጊነቱ ሲጨምር የኩባንያው ዋጋም ከፍ ይላል።
ምናልባት በሁለት ዶላር የገዙትን የኩባንያውን ድርሻ፣ አሁን ላይ በ4 ዶላር ሸጠው ትርፍ ሊያገኙ ይችላሉ።
#SouthEthiopia
" በእኛ ደረጃ የደረሰን ኦፊሻል መረጃ የለም። ቅሬታም የለም። ስለዚህ ዞኖቹን አናግራቸዋለሁ " - አቶ ወዳጀ ብዙነህ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ውስጥ በመዋቅር ጥያቄ ምክንያት " ወጣቶች በጅምላ ታስረው ይገኛሉ " ሲሉ የታሳሪ ቤተሰቦች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።
አንድ ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸው እዳይጠቀስ የጠየቁ ምንጭ፤ በቅርቡ ተዋቀረ ወደተባለው ኮሬ ዞን (የቀድሞው አማሮ ልዩ ወረዳ) የተካለለ ቦታ ወደ ዳኖ ማዕቀፍ እንዲመለስ የሚል ጥያቄ እንደተነሳ፣ በዚህም ማኅበረሰቡ ላይ ቅሬታ በመፈጠሩ ወጣቶች መንገድ ዘግተው ስለነበር የሃይማኖት አባቶች በሰጧቸው ምክር መንገዱ እንደተክፈተ ገልጸዋል።
መንገድ ዘጉ የተባሉትም ለምን እንደዘጉ ከሃይማኖት አባቶች ጥያቄ ሲቀርብላቸው 'እኛ መንገድ ለመዝጋት ፈልገን ሳይሆን ባለሥልጣናት መጥተው እንዲያወያዩን ፈልገን ነው' በማለት መንገዱን እንዲከፈት ተደርጓል ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶችም ሕዝቡ እንድታወያዩት ይፈልጋል ብለው ለባለሥልጣናቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።
በተያያዘም ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም እንደተጻፈ የሚያስረዳው ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ፣ ከዳኖ ቀበሌ የወጣው መዋቅር እንዲመለስ በመጠየቃቸው ምክንያት አሉታዊ ተፅዕኖ እየደረሰባቸው መሆኑና ሰዎች በተለይም ወጣቶችን እያሳደዱ የማሰር ተግባር መፈፀሙን ያስረዳል።
የታሳሪ ቤተሰቦች ሕዝቡን #ማወያየት ሲገባ መንገድ ያልዘጉ ወጣቶችን መንገድ ዘግታችኋል ተብለው በጅምላ ታስረዋል ያሉ ሲሆን መንገድ ተዘጋ ቢባል እንኳ አሁን የታሰሩት ሰዎች መንገድ የዘጉ እንዳልሆኑና ያለጥፋታቸው ከአንድ ወር በላይ እንደታሰሩ፣ በቀጠሯቸው ጊዜም ዳኞች እንደማይገኙ አስረድተው፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ፍትህ እንዲያሰጡ ጠይቀዋል።
ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ሁነቱን ያስረዱ ሌላኛው የዓይን እማኝ " ሦስት በአራት የሆነች ክፍል አለች እዚያ ውስጥ አንድ ላይ ነው ታራሚዎች የሚታጎሩት። እስር ቤቱ ውስጥ ላይ ደግሞ አያያዝ በጣም ያስጠላል ትኋን አለ፣ ቁንጫ አለ። በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህ ብቻ አይደለም እዚያ ከታሰሩት ሰዎች መካከል ተመርጠው ጥቆማ ለመስጠት የሚቀመጡ አሉ፣ ተንኮል ካሰቡ ሲፈልጉ አሳልፈው ለፖሊስ ይሰጣሉ። የተቀጠረው ተረኛ ፓሊስ በአንድ ግለሰብ ጥቆማ ብቻ መጥቶ ይቀጠቅጣል " ሲሉ አስረድተዋል።
ወጣቶች በጅምላ ታስረዋል መባሉን በተመለከተ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸው አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቀድሞ የአማሮ ልዩ ወረዳ ባለስልጣን ፣ በመዋቅር ጥያቄ ምክንያት ወጣቶች እደታሰሩና በቀጠሮ ቀንም ዳኞች ስለማይገኙ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) ከእስር እንዳልተፈቱ ገልጸዋል።
የኮሬ ዞን አስተዳደር፣ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ባለድርሻ አካላት ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ባይሆኑም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጥቷል።
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወዳጀ ብዙነህ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ " በእኛ ደረጃ የደረሰን ኦፊሻል መረጃ የለም። ቅሬታም የለም። ስለዚህ ዞኖችን አናግራቸዋለሁ " ብለዋል።
አክለውም፣ ቅሬታ በቀረበበት መንገድ የታሰሩበት ሁኔታ በፍጹም ትክክል እንዳልሆነ ገልጸው፣ " እንዲህ አይነት ችግሮችን ቢያንስ የመዋቅር ዞኑ አልፈታ ካለ እኛ ጋ ማድረስ ነበረባቸው አሰራሩም እንደዛ ነው። እኛ ቼክ እናደርጋለን " የሚል ምላሽ ሰጥዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በጉዳዩ ዙሪያ ክትትል እንደተደረገና የእስር ቤት አያያዝ ሁኔታው የሚገለጸው ኮሚሽኑ በሚያወጣው ሪፓርት እንደሆነ አስረድቷል።
#ስፖርት : ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ ሻሚዮንስ ሊግ ፍጻሜ ቦሪስያ ዶርትመንድን በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆነ።
ቡድኑ እጅግ ጠንካራ ነው የሚባለውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በተደጋጋሚ አሸንፏል።
ቡድኑ በታሪኩ ይህን ዋንጫ ሲያሸንፍ 15ኛ ጊዜ ነው።
ይህ የእግር ኳስ ፍልሚያ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በወጣቶች ዘንድ እንዲሁም በመላው ዓለም በርካታ ሚሊኒዮን ተመልካች ያለው ሲሆን ምርጥ የሚባሉት የአውሮፓ ክለቦች የሚሳተፉበት ነው።
#Adama
ተከሳሽ ቶሎሳ ወይም ፍቅሩ አሸናፊ ይባላል።
በአዳማ ከተማ ቦሌ ክፍል ከተማ በተለምዶ ደካ አዲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም እናቱን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል።
ተከሳሹ እናቱን በስለት (ቢላዋ) በአሰቃቂ ሁኔታ ወግቶ ነው ህይወታቸውን እንዲያጡ ያደረገው።
ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመው #በቁማር_የተበላዉን ገንዘብ እናቱ ያላቸውን ንብረት በመሸጥ እንዲተኩለት ለማድረግ ሲል እየደበደበ ያሰቃያቸው እንደነበር ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ አረጋግጧል።
በዚህ ብቻ ያላበቃው ተከሳሽ ሚያዚያ 21/ 2016 ዓ/ም ጠዋት በአሰቃቂ ሁኔታ የእናቱ ህይወት እንዲያልፍ በማድረጉ ከባድ የግድያ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
ጉዳዩን የተመለከተው የአዳማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት በሞት እንዲቀጣ ወስኗል።
በተከሳሹ ላይ የተጣለው #የሞት_ፍርድ በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሲጸድቅ ነው ተፈጻሚ የሚሆነው። #ቢቢሲ
#Oromia
ኢሰመኮ ፦
- ታኀሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጉዱሩ ወረዳ ውስጥ በተፈጸመ #የድሮን_ጥቃት ፦
° በየነ ጢቂ፣
° ጉደታ ፊጤ፣
° ሀብታሙ ንጋቱ፣
° ታዴ መንገሻ፣
° ዳመና ሊካሳ፣
° ዱጋሳ ዋኬኔ፣
° ሕፃን አብዲ ጥላሁን
° ሕፃን ኦብሳ ተሬሳ የተባሉ 8 ሰዎች ተገድለዋል።
በተጨማሪም፦
• ስንታየሁ ታከለ፣
• ሽቶ እምሩ፣
• ተሜ ኑጉሴ
• አለሚ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአካባቢው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ #ኦነግ_ሸኔ ”) በሰፊው ይንቀሳቀስ የነበረ መሆኑን እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው በሚደረጉ ውጊያዎች አልፎ አልፎ #በድሮን_ይጠቀም የነበረ መሆኑን ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
- ጥር 9/2016 ዓ/ም በሰሜን ሸዋ ዞን ፤ ደራ ወረዳ የሀገር መከላከያ ሰራዊት #ለሌላ_ግዳጅ አካባቢውን ለቅቆ ይወጣል። ይህን ተከትሎም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ ሸኔ) ታጣቂዎች በማግስቱ አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ “ ለመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ምግብ ስታቀርቡ ነበር ” በማለት 01 ቀበሌ የሚገኘው ሳላይሽ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ጥበቃ የነበሩት አቶ ስዩም ካሴን #በጥይት_በመምታት ገድሏል። አቶ ከበደ ዓለማየሁ የተባሉ ነዋሪን ከመኖሪያ ቤታቸው አስወጥተው ከወሰዷቸው በኋላ በአካባቢው ጫካ አስክሬናቸው ወድቆ ተገኝቷል።
- ጥር 13 ቀን 2016 ዓ/ም ከጠዋት 2 ሰዓት ጀምሮ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች በምዕራብ ጉጂ ዞን፣ ገላና አባያ ወረዳ ኤርገንሳ ቀበሌ ለሚኖሩ ነዋሪዎች የኩፍኝ በሽታ ክትባት ለመስጠት በመጓዝ ላይ በነበሩ ሠራተኞች ላይ በፈጸሙት ጥቃት የገላና አባያ ወረዳ አስተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊን ጨምሮ ሁለት ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል። እንዲሁም 3 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
- ከየካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ #የአማራ_ታጣቂ_ቡድኖች የኦሮሚያ ክልል ፤ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በሚገኙ አዋሳኝ ቀበሌዎች በሲቪል ሰዎች ላይ #በተከታታይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች ፦
➡️ 25 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል ፤
➡️ 4 ሲቪል ሰዎች ላይ የአካል ጉዳትን አድርሰዋል
➡️ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሲቪል (ሰላማዊ) ሰዎችን #አግተው ወስደዋል። በታጣቂዎቹ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ የመኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል።
- በሰሜን ሸዋ ዞን ፤ ደራ ወረዳ የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶው “ ኦነግ ሸኔ ”) ታጣቂዎች ከኅዳር ወር 2016 ዓ/ም ጀምሮ በወረዳው በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች ፦
➡️ 15 ሲቪል (ሰላማዊ) ሰዎች #ተገድለዋል ፤
➡️ ቁጥራቸው ለጊዜው በትክክል ያልታወቀ በርካታ ነዋሪዎችን #አግተው_ወስደዋል ፤
➡️ በርካታ የቀንድ ከብቶችን ዘርፈዋል
➡️ መኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል።
- መጋቢት 1/2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ስልካምባ ከተማ ላይ የኦሮሞ ነጸነት ሰራዊት (በተለምዶ “ #ኦነግ_ሸኔ ”) ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት የወረዳው አበዪ ሄቤን ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አቶ ሹመቴ ፋርስ እና ወ/ሮ ተቀባ አበጋዝ የተባሉ አረጋዊያን በመኖሪያ ቤቶቻቸው ፊት ለፊት ተገድለዋል።
- መጋቢት 16/2016 ዓ/ም ከምሽቱ 3፡00 እስከ 5፡00 ባሉት ሰዓታት ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ቡድኖች በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ 02 ቀበሌ ውስጥ 7 ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን ለማወቅ ተችሏል። በዕለቱ በተፈጸመ ጥቃት የቀበሌው ነዋሪ የሆነ እና የምዕራብ አርሲ ሃገረ ስብከት የዶዶላ ደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆነ ግለሰብ ፣ ከባለቤቱ እና #ከ2_ልጆቹ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው እያሉ እንዲሁም ሌላ አንድ ዲያቆን ከባለቤቱ እና ከእህቱ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
- መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ/ም በዶዶላ ወረዳ በደነባ ቀበሌ በግምት ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ላይ 4 የቀበሌው ነዋሪዎች ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ሰዎች/ቡድኖች በጥይት ተመተው ሲገደሉ 5 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
- የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ( በተለምዶ “ #ኦነግ_ሸኔ ” ) በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ወረዳ ውስጥ “ የመንግሥት ሠራተኞች እና የመንግሥት ጸጥታ ኃይል አባላት ቤተሰቦች ናችሁ ” በሚል ወይም “ለመንግሥት አካላት ትብብር አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች በየካቲት እና ሚያዝያ ወራት በፈጸማቸው ተከታታይ ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ እገታ፣ ንብረት ውድመት እና ዘረፋ ፈጽሟል።
ለምሳሌ ፦
👉 በወረዳው አቡዬ ጀብላል ቀበሌ የካቲት 7/ 2016 ዓ.ም. በፈጸመው ጥቃት 11 ሲቪል ሰዎችን ገድሏል፤ መኖሪያ ቤቶችንና ሞተር ብስክሌቶችን አቃጥሏል፤ የቀንድ ከብቶችን ዘርፏል።
👉 መጋቢት 27/2016 ዓ.ም. በወረዳው ቆታ ከተማ ላይ በፈጸመው ጥቃት 31 ሲቪል ሰዎችን ገድሏል፣ 3 ሲቪል ሰዎችን አቁስሏል፣ የቀንድ ከብቶችንና ሌሎች ንብረቶችን ዘርፏል እንዲሁም ንብረቶችን አቃጥሏል።
👉 ሚያዝያ 8/2016 ዓ/ም በደራ ቲርቲሪ ቀበሌ ላይ ታጣቂ ቡድኑ በፈጸመው ጥቃት 2 ሲቪል ሰዎችን ገድሏል ፣ ከ100 በላይ የተለያዩ የቀንድ ከብቶች ዘርፏል።
👉 በሚያዝያ 13/2016 ዓ/ም በጎምንቦሬ አሊይ ቀበሌ 36 የቀንድ ከብቶችንና 3 የሞቶር ብስክሌት ዘርፏል።
#የመውጫፈተና #ምረቃ
➡️ " ትምህርታችን በአግባቡ ብንጨርስም ለ8 ወራት ትዘገያላችሁ ተብለናል " - ተማሪዎች
➡️ " ይህ ውሳኔ የመጣዉ #ከትምህርት_ሚኒስቴር በመሆኑ ምንም ማድረግ አልቻልንም " - የኮሌጅ አመራሮች
➡️ " የመጀመሪያ ዲግሪ የሚማሩ ተማሪዎች የተቋም ቆይታቸው ቢያንስ 4 ዓመት ነው " - ትምህርት ሚኒስቴር
ከሰሞኑን በርካታ #የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከምረቃ እና ከመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የቅሬታ መልዕክቶችን ልከዋል።
ቅሬታቸውን ከላኩት መካከል በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ ደሴ እና ሌሎች ከተማ የሚገኙ የኮሌጅ ተማሪዎች ይገኙበታል።
ተማሪዎቹ " በ4 አመታት ውስጥ ማጠናቀቅ ያለብንን ትምህርታችን በአግባቡ ጨርሰን ፤ ክሊራንስም ሆነ የመውጫ ፈተና ለመውሰድ ክፍያ ብንፈጽምም ድንገት ለ8 ወራት መቆየት አለባችሁ ተባልን " ሲሉ ገልጸዋል ።
ቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎቹ ፦
° ከሌሎች ተመራቂ ተማሪዎች እኩል በሚባል ደረጃ ትምህርት እንደጀመሩ፤
° መወሰድ የሚጠበቅባቸው አስፈላጊውን ኮርስ ወስደው ማጠናቀቃቸውን፤
° የመዉጫ ፈተና የማዘጋጃ ቲቶሪያል መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ይሁንና " የመዉጫ ፈተናዉን ልንወስድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩን የመመረቂያ ቀናችሁ ጊዜ በሚቀጥለዉ ዓመት ጥር ላይ ነው " በማለት የመውጫ ፈተናውን መውሰድ እንደማይጠቅመን እና የሀምሌ ወር ምረቃችን መሰረዙ ተነገረን ሲሉ ቅሬታቸዉን ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ " ተመሳሳይ ባች ከሆኑ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እኛ በምን ተለይተን ነው ይሄ የተደረገው ? ለምን ሌላው ሊፈተን ሲዘጋጅ እኛ ግን ' ብትፈተኑም ጥቅም የለውም ቀጣይ ዓመት ጠብቁ ' ተባልን ? ይህ በፍጹም አግባብነት የለውም ፤ መፍትሄ እንሻለን " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያም ከደረሱት ብዛት ያላቸው ቅሬታዎች በመነሳት ኮሌጆችን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል።
ከነዚህም ውስጥ አንዱ ተማሪዎቹ የሚጠበቅባቸዉን ኮርስና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ማጠናቀቃቸዉን ልክ እንደሆነ ገልጿል።
ይሁንና የመመረቂያ ጊዜያቸዉ የተወሰነዉ ከትምህርት ሚኒስቴር በመጣ አቅጣጫ መሆኑን አስረድቷል።
ኮሌጁ ፤ ተማሪዎቹ #የተፈተኑበት_ጊዜ ምንም እንኳን 2012 ዓ/ም መሆኑን በወቅቱ ከትምህርት ሚኒስቴር በኩል ያገኙት 'የኦንላይን ዶክሜንት' ቢያሳይም በኋላ የመጣላቸዉ ኦሪጅናል ደግሞ 2013 ዓ/ም እንደሚል ገልጿል።
ይህም ደግሞ ተማሪዎቹን ወደኋላ እንደሚያቆያቸዉና ለሚቀጥሉት ወራት የተለያዩ ትሬኒጎችና የመዉጫ ፈተና መለማመጃዎች እየሰጡ ለማቆየት መታሰቡን አስረድቷል።
በሌላ በኩል ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር ለተለያዩ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተላከ አንድ ደብዳቤ ተመልክተዋል።
ደብዳቤው ፦
በ2013 ዓ/ም ሁለተኛ ሴሚስተር ትምህርት የጀመሩ ተማሪዎች ለሰኔ ወር 2016 ዓ/ም የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ እንዲደረግላቸው የጠየቁ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዳሉ ያስረዳል።
ነገር ግን የትምህርት ሥልጠና ፓሊሲው የመጀመሪያ ዲግሪ የሚማሩ ተማሪዎች የተቋም ቆይታቸው ቢያንስ 4 ዓመት እንደሆነ እንደሚደነግግ ይገልጻል።
አንዳንድ ተቋማት ህጋዊ ባልሆነ አግባብ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ መጠየቃቸውን በማንሳት ይህ የሚያስጠይቅ ነገር ስለሆነ ተቋማት ተማሪዎችን በአግባቡ በማብቃት የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ እንዲሰሩ አስጠንቅቋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተጨማሪ መረጃዎችን ከትምህርት ሚኒስቴር በኩል ጠይቆ ለማቅረብ ጥረት ያደርጋል።
" የሃይማኖት ጉዳዮች " ረቂቅ አዋጅ ምን ይዟል ?
በኢትዮጵያ አዲስ የተዘጋጀ " #የሃይማኖት_ጉዳዮች " ረቂቅ አዋጅ አለ። ይህ ረቂቅ አዋጅ በርካታ ጉዳዮችን ይዟል።
አንዱ የአምልኮና የመቃብር ቦታን የተመለከተ ሲሆን ፥ ረቂቅ አዋጁ ለሃይማኖት ተቋማት የመሬት አቅርቦት በመሬት አጠቃቀምና የሊዝ ሕጎች መሠረት ይወሰናል ይላል።
ለአምልኮ ወይም ለመቃብር ቦታ በተጠየቀበት አካባቢ ለሃይማኖት ተቋሙ ለተመሳሳይ ዓላማ የተሰጠ ቦታ አለመኖሩ ወይም ደግሞ #ተጨማሪ_ቦታ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበትም ይገልጻል።
በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል ላይ የሚኖረው ርቀት ቢያንስ 500 ሜትር መሆን አለበትም ይደነግጋል።
ትምህርትና የሃይማኖት ተግባራትን በተመለከተ ረቂቁ ፥ መደበኛ ትምህርት በሚሰጡ የመንግሥት / የግል ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ሃይማኖታዊ ይዘት የሌለው መሆን አለበት ይላል።
በትምህርት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርትን ማስተማር ወይም በቡድን ማምለክ ፈጽሞ የተከለከለ ስለመሆኑ ይገልጻል።
ሌላውረቂቁ ማንነትን ለመለየት ሚያስችሉ ሃይማኖታዊ አለባበሶችን ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደማይገባ ይደነግጋል።
ከአለባበስን ጋር በተያያዘ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት " ሃይማኖታዊ ምልክቶችን እንደ ቤተ እምነቱ አስገዳጅ ሕግጋቶች #ልዩ_ሁኔታዎች እንደሚኖሩ መደንገግ ሲገባው፣ ሙሉ ለሙሉ ከትምህርትና ሥራ ገበታ የሚያስገድዱ ድንጋጌዎችን መያዙ አግባብ አይደለም " በማለት ለሰላም ሚኒስቴር አስተያየት ፣ ቅሬታ እና የመፍትሔ ሐሳብ ልኳል።
የመንግስት ስራ ኃላፊዎችን በተመለከተ መንግሥትን ወክለው በሃይማኖት በዓላት አከባበር ላይ መገኘት እንደማይችሉ ተቀምጧል።
በየት/ቤት ፣ በመኖሪያ ቤት እና በሕክምና ማዕከላት አካባቢ የሚደረግ አምልኮ በተመለከተም ፤ በአካባቢ ጥበቃ ሕግ የተቀመጠውን የድምፅ መጠን ያከበረ መሆን አለበት ይላል።
ካልተፈቀደ በስተቀር ማስተማርን ጨምሮ ሃይማኖታዊ ተግባራትን በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች መፈጸም እንደማይቻልም ተቀምጧል።
የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ይህ በልዩ ሁኔታ በወንጌል አማኞች ላይ ጫና የሚፈጥርና ሕገ መንግሥታዊ የሆነ መሠረት የሌለው በመሆኑን መስተካከል ይኖርበታል በማለት ለሰላም ሚኒስቴር ደብዳቤ ልኳል።
#ሪፖርተርጋዜጣ
#INSA #ጥቆማ
የብሔራዊ የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ምዝገባ መካሄድ ጀምሯል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በ2014 ዓ/ም እና በ2015 ዓ/ም ለሁለት ተከታታይ አመታት በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች በክረምት ፕሮግራም (Summer Program) አሰልጥኖ ማስመረቁን ገልጿል።
ተመራቂዎችንም ፦
° #እንደየችሎታቸው እና #እንደስራዎቻቸው ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር የማስተሳሰር፤
° ኢመደአን (INSA) ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት #ተቀጥረው መስራት የሚችሉበት ሁኔታ እንዳመቻቸ አመልክቷል።
ባለፉት ሁለት አመታት የተከናወኑ የሳይበር ታለንት ልማት ፕሮግራሞችን መነሻ በማድረግ በ2016 በጀት አመት “ብሄራዊ የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ” ፕሮግራም መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የዚህ ቻሌንጅ ዋና ዓላማ በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ መስኮች ልዩ ተሰጥዖ ያላቸዉን ሰዎች በመመልመል በዘርፉ ላይ ተጨባጭ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል ብሄራዊ የሳይበር ሰራዊት (National Cyber Army) መገንባት ነው ተብሏል።
በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ እና ፍላጎት ያላቸው እና እድሜያቸው ከ11 አመት ጀምሮ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዚህ ቻሌንጅ ላይ መሳተፍ ይችላሉ ተብሏል።
መመዝገቢያ ጊዜ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ነው።
መመዝገቢያ አድራሻው https://talent.insa.gov.et ነው።
" ሞቶ የመገኘቱ ጉዳይ እንቆቅልሽ ነው የሆነብን " - የጋዜጠኛው ጓደኞችና የስራ ባልደረቦች
የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት የሆሳዕና ቅርንጫፍ ጋዜጠኛ የሆነው አብይ አበራ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ስርአተ ቀብሩም በትዉልድ መንደሩ በአንጋጫ ወረዳ ፉነሙራ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።
ወጣቱ ጋዜጠኛ አብይ ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ተቀጥሮ ሲሰራ በጠንካራ አቋሙና በታታሪነቱ የሚታወቅ ቢሆንም ከሰሞኑ በቤቱ ውስጥ ሞቶ መገኘቱን ተከትሎ በቤተሰቦቹ በጓደኞቹ እና በስራ ባልደረቦቹ ላይ ታላቅ ድንጋጤ የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል።
በጋዜጠኝነት ስራ ላይ የሚያዉቁት ጓደኞቹ ስለታላላቅ ህልሞቹ የሚናገሩለት አብይ ትናንት ጠዋት ሞቶ የመገኘቱ ጉዳይ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸዉ ገልጸዋል።
ለቲኪቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን የሰጡ የጋዜጠኛው ጓደኞች እና የስራ ባልደረቦች ፥ " አብይ ራስን የማጥፋት ተግባር ይፈጽማል ብለን ፈጽሞ አናስብም " ብለዋል።
ከጋዜጠኝነት ስራው ባለፈ ራሱን ለመደገፍ ማንኛዉንም ስራ በመስራቱ ለብዙዎች አርአያ መሆኑን የሚናገሩት ባልደረቦቹ በቅርቡ የራሱን ምግብ ቤት ከፍቶ በሰዎች ሲያሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።
ላመነበት ጉዳይም ወደኋላ የማይል ጠንካራ አቋም ያለዉ ሰው መሆኑን ተከትሎ " የአሟሟቱ ጉዳይ እንቆቅልሽ ሆኖብናል " ብለዋል።
ይህን ጉዳይ ይዘን ያነጋገርናቸዉ የጸጥታ አካላት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ምላሽ ምንም ፤ ሁኔታዉን ለማጣራት አስከሬኑ በተገኘ ቅጽበት ወደ ወራቤ ሪፈራል ሆስፒታል ለምርመራ መላኩን ገልጸዋል።
ፖሊስ ፤ ጋዜጠኛው ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ሞቶ የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ ከአስከሬን ምርመራዉ በተጨማሪም ሌሎች የማጣራት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና የሚገኘዉን ውጤት እንደሚሳውቅ ተናግሯል።
" ሲጀመር ‘የኮቴ’ ክፍያ አገር ውስጥ መጠየቅ አግባብ አይደለም " - ጣና የከባድ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ማኀበር
የከባድ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ፣ ሞጆ መግቢያ ‘ #የኮቴ ’ በሚል ታጣቂዎች አስቁመው 2,000 ብር እያስከፈሏቸው መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ።
ካሁን ቀደም ገንዘቡን ሲጠየቋቸው የነበረው አንዳንድ ጊዜ በቀን እንደነበር ፣ ከሰሞኑን ግን ቀንም ሌሊትም እየጠየቋቸው ከመሆኑም ባሻገር ድብደባና እንግልት እያደረሱባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ሰሞኑን አንዱን ሹሬር ሞጆ መግቢያ ከሌሊቱ 6 ሰዓት አስቁመው ገንዘብ እንደጠየቁት፣ ‘የለኝም’ ሲላቸው እንዳንገላቱት ገልጸዋል።
ሌላኛው ሹፌር ክፉኛ መመታቱን አመልክተዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ስለ “ ኮቴ ” ክፍያው ምንነት ያውቅ እንደሆን የጣና የከባድ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ማኀበርን ጠይቋል።
ማኀበሩ ፤ " አሁን #ጂቡቲ ስንደርስ የሌላ አገር መሬት ስለምንረግጥ ‘ የኮቴ ’ እንከፍላለን። የተለመደ ነው። እዚህ ግን ‘የኮቴ’ እያሉ 2,000 ነው የሚጠይቁት። ይሄ ደግሞ ተገቢም አይደለም " ብሏል።
" ሞጆ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ድርጊቱ አለ " ያለው ማኀበሩ ፣ አንድ ጊዜም ቢሆን መከፈሉ ከህግ አግባብ ውጪ ሆኖ ሳለ በድጋሚ ሌላ ቦታ ላይ እንደሚያስከፍሏቸው አስረድቷል።
ማኀበሩ ፤ " ሲጀመር ‘ የኮቴ ’ ክፍያ በአገር ውስጥ መጠየቅ አግባብ አይደለም " ብሎ፣ ከክፍያው ባሻገር አሽከርካሪዎቹ ገንዘቡን በሚጠይቁ መሳሪያ የታጠቁ ታጣቂዎች ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው፣ የክልሉ አካላት ድርጊቱን ቢያውቁም መፍትሄ እንዳልሰጡ ገልጿል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፤ ቅሬታውን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ወደ ክልሉ ባለስልጣናት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።
Video Credit - ኪያ
#Palestine
ዛሬ አይርላንድ ፣ ኖርዌይ እንዲሁም ስፔን ለፍልስጤም የነጻ ሀገርነት እውቅና እንደሚሰጡ በይፋ አስታወቁ።
" የዛሬው ቀን ለፍልስጤም እጅግ ታሪካዊ ቀን ነው " ተብሏል።
የአየርላንድ ጠ/ሚኒስትር ሲሞን ሃሪስ " ዛሬ አየርላንድ ፣ ኖርዌይ እና ስፔን ለፍልስጤም የነጻ ሀገርነት እውቅና ሰጥተናል። ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ እያንዳንዳችን ማንኛውንም አይነት ብሔራዊ እርምጃ እንወስዳለን " ብለዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ ፥ " #በሚቀጥሉት_ሳምንታት ተጨማሪ ሀገራት ይህን ጠቃሚ እርምጃ ለመውሰድ ከእኛ ጋር እንደሚተባበሩ እርግጠኛ ነኝ " ሲሉ አክለዋል።
የአይርላንድ መንግሥት ይህ የሀገርነት እውቅና የሁለት ሀገር መፍትሄን እንደሚደግፍና ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እና የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ኢስፔን ባርት ኢይድ ሀገራቸው ከግንቦት 28 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ለፍልስጤም ግዛት እውቅና እንደሚሰጡ በይፋ አሳውቀዋል።
የስፔኑ ጠ/ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ፥ " ምንም እንኳን ከአሸባሪው ቡድን #ሃማስ ጋር የሚደረገው ውጊያ ህጋዊ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ለፍልስጤም የሰላም ፕሮጀክት የላቸውም " ብለዋል።
የኖርዌይ ጠ/ ሚኒስትር ጆናስ ጋህር ስቶር በበኩላቸው ፥ " እውቅና ከሌለ (የፍልስጤም) በመካከለኛው ምስራቅ ምንም ሰላም ሊኖር አይችልም " ብለዋል።
" ሽብር የተፈፀመው በሃማስና የሁለት ሀገር መፍትሄን በማይቀበሉ እንዲሁም የእስራኤልን መንግሥት በማይደግፉ ታጣቂ ቡድኖች ነው። " ሲሉ አክለዋል።
" ፍልስጤም ነጻ አገር የመሆን መሠረታዊ መብት አላት " ብለዋል።
የፍልስጤም #የነጻ_ሀገርነት እውቅና መስጠት በይፋ ከተሰማ በኃላ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር #በኖርዌይ እና #በአይርላንድ የሚገኙ አምባሳደሮችን በአስቸኳይ ወደ እስራኤል እንዲመለሱ አዘዋል።
ሚኒስትሩ፤ " የዛሬው ውሳኔ ሽብርተኝነት እንደሚከፍል ለፍልስጤማውያን እና ለዓለም መልእክት ያስተላለፈ ነው " ብለዋል።
መረጃው የስካይ ኒውስ ነው።
More - @thiqahEth
ዛሬ ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡30 ሰዓት ገደማ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ላይ የዕሳት አደጋ ተከስቶ እንደነበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሳውቋል።
እሳቱ የተፈጠረው ከአውሮፕላን ማረፊያው አጥር ውጭ ባሉ የመኖሪያ ቤቶች ውስጥ እንደነበረ ገልጿል።
አሁን ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉንም አመልክቷል።
" በኢትዮጵያ አየር መንገዱ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ምንም ዓይነት መስተጓጎል አልነበረም " ሲልም አክሏል።
#Update
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት እነ ቀሲስ በላይ መኮንን ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ አዟል።
በዋስ ጥያቄያቸው ዛሬም ውድቅ ተደርጓል።
ቀሲስ በላይ መኮንን በችሎቱ ፥ " ፖሊስ ይዞኝ ሳይሆን እራሴ ነው የሄድኩት " ብለዋል፡፡
" #ብዙ_የሀገር_ጉዳይ በእጄ ስላሉ ጥፋ ብባል እንኳ የምጠፋ ስላልሆንኩ ፤ በጤናዬ ላይ በደረሰው እክልና በቤተሰቦቼ ላይ በደረሰው ችግር ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ይጠብቅልኝ " ሲሉ ጠይቀዋል።
የብዙ ልጆች አሳዳጊና የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆኑ ጠቅሰው በዋስ ከእስር እንዲወጡ ጠይቀው ነበር።
ፍርድ ቤት ግን ሁሉም ተከሳሾች በፖሊስ ጣቢያ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ አዟል።
ቀሲስ በላይ መኮንን በሀሰተኛ ሰነድ ከአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ላይ #ከ6_ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማውጣት ሙከራ አድርገዋል ተብለው አብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች ጭምር መታሰራቸው አይዘነጋም።
ያንብቡ : https://telegra.ph/DW-05-20 #ዶቼቨለ
በኢራን የሂሊኮፕተር አደጋ የሞቱት እነማን ናችው ?
- የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ
- የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር አብዶላሂያን
- የተብሪዝ መስጂድ ኢማም አያቶላህ አልሃሸሚ
- የምስራቅ አዘርባጃን ግዛት አስተዳዳሪ ማሊክ ራህማቲ
- የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ ኃላፊ ማሄዲ ሙሳቪ
- የሄሊኮፕተሩ አብራሪ፣
- የሂሌኮፕተሩ ረዳት አብራሪ
- ቦዲጋርድ
- የበረራ አስተናጋጅ በትላንቱ የሂሊኮፕተር አደጋ ሞተዋል።
የፕሬዜዳንት ራይሲን ሞት ተከትሎ ምክትል ፕሬዜዳንቱ ሞሀመድ ሞክበር በ50 ቀናት ውስጥ በምርጫ አዲስ ፕሬዜዳንት እስኪመረጥ ድረስ የፕሬዜዳንቱን ቦታ ተክተው ይሰራሉ።
#AddisAbaba
አምስት (5) ፓርኮችን ለማልማት ከ10 ቢሊዮን ብር ላይ የሚፈጅ የፕሮጀክት ጥናት መደረጉ ተነገረ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ መዝናኛ ኮርፓሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 10 ፓርኮች መካከል 5ቱ በንጉሱ እና በደርግ ጊዜ የተሰሩና ከስታንዳርድ በታች በመሆናቸው ለማልማት / ደረጃቸውን ለማሻሻል ታቅዶ ለ3ቱ ዲዛይን ተሰርቶ አንዱን ማልማት መጀመሩን አስታውቋል።
ኮርፓሬሽኑ ይህንን ያለው ባለፈው ቅዳሜ በሰጠው መግለጫ ሲሆን የሚታደሱትም ፦
- ኩባ ፓርክ፣
- ሐምሌ 19፣
- ብሔረ ፅጌ፣
- ኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ፣
- አዲስ ዙ (ፒኮክ) ፓርኮች መሆናቸውን ገልጿል።
ለማልማት ምን ያህል በጀት ያስፈልጋል ? ተብሎ ጥያቄ የቀረበለት ኮርፖሬሽኑ ፥ “ Estimation በጀቱ ትልቅ ነው። የኮንስትራክሽን በጀቶቹ ቀላል አይደሉም ” ብሏል።
“ አሁን አዲሱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ፕሮጀክት ነው የተጠናው። በተግባር ሲገባ ስንት ይሆናል ? የሚለው በወቅቱ የምናሳውቅ ይሆናል። ኮሪያ ፓርክ ላይም እየሰራን ያለነው ከ100 ሚሊዮን ብር ባለፈ ወጪ ያለው ነው ” ሲልም አክሏል።
' ስድስት ኪሎ ' ያለው ፓርክ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ሲታደስ የታሪክ ትዝታዎቹ አይጠፉም ወይ ? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም፣ “ 6 ኪሎም ሆነ ሌሎቹን በፊት ያለውን መሠረታዊ ነገር እንዲለቅ አይፈለግም ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
“ የፓርኮች ልማት ጤናማ የሆነ ማህበረሰብ እንዲኖር የማድረግ እድል ይኖረዋል። ስለዚህ በእኛ በኩል ከማንኛውም ልማት በላይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራው፣ ሕዝብንና ተፈጥሮን የማገናኘት ጉዳይ ነው የፓርክ ጉዳይ ” ብሏል ኮርፖሬሽኑ።
“ የፓርክ ልማት ለአዲስ አበባ የህልውና ጉዳይ ነው። ትርፍ ስራ አይደለም ፤ የ Prioritization ስራም አይደለም ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ፤ አለበለዚያ ከተማው በአንድ ጀንበር የመጥፋት እድል ነበረው ” ሲል ገልጿል።
“ በዛ መልክ የማንሰራ ከሆነ የከተማው ህልውና አደጋ ላይ ነው ያለው። የማህበረሰቡ አኗኗር ለበሽታ የመጋለጥ እድሉ በጣም ከፍተኛ ነው። ፓርክ መስራት ማለት ለሕዝቡ ኦክስጂን መስጠት ነው ” ነው ያለው።
በቀጣይም በኮሪደር ልማት ስራ በርካታ ፓርኮች እና መዝናኛ ቦታዎች እንደሚሰሩ ያመለከተው ኮርፖሬሽኑ እነዚህንም በማካተት " የህዝቡን የመዝናኛ እና ንጹህ ቦታ የመኖር ፍላጎት እንዲሟላ እንሰራለን " ብሏል።
🔹 " እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ሙስና የሚፈጸመው #በኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው " የመ/ግ/ን/ባ
በመንግሥት የግዥ ሒደት እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ሙስና የሚፈጸመው በኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑን፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ይህን ያስታወቀው ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በዘንድሮ በጀት ዓመት በ169 የፌዴራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሲስተም ተግባራዊ ተደርጎና አፈጻጸሙን ለማሳደግ፣ ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ነው፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ምን አሉ ?
- በመንግሥት በግዥ ሥርዓት ውስጥ፣ ከ80 እስከ ከ90 በመቶ በላይ ሙስና የሚፈጸመው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው ብለዋል።
- ስሙን መጥቀስ ያልፈለጉት የመንግሥት ተቋም #በጨረታ አንደኛ የወጣ ድርጅት እያለ ሦስተኛ ከወጣው ጋር ውል መግባቱን፣ በዚህም ምክንያት ባለሥልጣኑ እስከ ፍርድ ቤት በመሄድ ሒደቱ እንዲቋረጥ ማደረጉን ገልጸዋል፡፡
- ከኮንስትራክሽን ጋር ተያይዞ ጨረታ የሚያወጡ የመንግሥት ተቋማት #የሚፈልጉዋቸው ተጫራቾች ካልመጡ እስከ #መሰረዝ እንደሚደርሱ አመልክተዋል።
- የመንግሥት ተቋማት ተጫራቾችን ሆን ብለው ከጨረታ ውጪ እንዲሆኑ ሕጎችን እንደ ምክንያት እንደሚጠቀሙ፣ ያሸነፉ ተጫራቾችንም #እንዲሰላቹ በማድረግ ከጨረታ ውጪ እንዲሆኑ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
- በመንግሥት የግዥ ሥርዓት ምክንያት የሚመጡ ክሶች መኖራቸውን ገልጸው በዓመት እስከ 150 የሚደርሱ ክሶች እንደሚስተናግዱ ተናግረዋል። በአብዛኛው ጨረታ የማውጣትና የሚገመገምበት መሥፈርት በመለያየቱ ምክንያት በርካታ ተጫራቾች ክስ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢጋድ አባል አገሮችና የነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ እንግዳዬ እሸቴ ምን አሉ ?
- በኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ከታዩ ክፍተቶች አንዱ በጠቅላላ የመንግሥት ግዥ መባሉ ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል።
- የመንግሥት ግዥ ተብሎ ስያሜ ቢሰጠውም የመንግሥት ተቋማትና የንግዱ ማኅበረሰብ የሚገናኙ በመሆናቸው ከስያሜ ጀምሮ ማስተካከያ ይፈልጋል ብለዋል።
- የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ሙስናን ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጻዋል። ከዚህ ቀደም #በዩኒቨርሲቲዎች በሚደረጉ ግዥዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች እየቀረቡ እንደነበርና ሥርዓቱ መዘመኑ በተወሰነ መንገድ ችግሩን መቀረፉን አስረድተዋል፡፡
- በኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ለሚታዩ የሙስና ብልሹ አሠራርን ከሥሩ ማድረቅ እንደሚገባ፣ በተለይ ተጫራጮች ወደ ተቋማት ሲሄዱ #ሲስተም_የለም የሚለው ቋንቋ የችግሩ መጀመርያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
- ተጫራቾች ወይም የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ለሙስና እንዳይጋለጡ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ ሞጋችና ተከራካሪ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የመንግሥት ግዥ የንብረት ባለሥልጣን የመንግሥት ግዥ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ከበደ ምን አሉ ?
- የነባሩ የወረቀት የግዥ ሥርዓት የሙስና ተጋላጭነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እየተደረገበት ነው ብለዋል።
- የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት መኖሩ የሚቀርፏቸው ችግሮች ሰፊ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ለብዙ ተጫራቾች ዕድል ከመስጠት አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
- የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት በ2015 ዓ.ም. ሲጀመር የተመዘገቡት የንግድ ማኅበረሰብ አባላት 100 ብቻ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በጥቅሉ ከ15‚000 በላይ ተሻግረዋል።
- ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ በጀቷ 70 በመቶ የሚውለው ለግዥ ሥርዓት መሆኑን ገልጸው ይህም በገንዘብ ሲቀየር 560 ቢሊዮን ብር ለግዥ እንደሚውል ተናግረዋል።
#Reporter
#Tigray
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕረዚደንት ጌታቸው ረዳ ተጫማሪ አራት ከፍተኛ አመራሮችን ከስልጣን አነሱ።
ከስልጣን ያነሷቸው ፦
- አቶ አለም ገ/ዋህድ የህወሓት የፓለቲካዊ ጉዳዮች ሃላፊና ዋና ፓሊት ቢሮ አባል ከጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕረዚደንት አማካሪ
- የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ሊያ ካሳ ከደቡባዊ ምስራቅ ዋና አስተዳዳሪ
- የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል አቶ ተኽላይ ገ/መድህን ከሰሜናዊ ምእራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ
- የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል አቶ አማኒኤል አሰፋ ከጊዚያዊ አስተዳደር ቺፍ ካቢኔ ሰክሬታሪያት ነው።
በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ተፅፎ ቁጥር ፣ ማህተምና ቲተር ያረፈበት ደብዳቤ እንደሚያመለክተው አራቱ ከፍተኛ አመራሮች ለሰጡት መንግስታዊ አገልግሎት በማመስገን ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ከጥቅምት 15/2016 ዓ.ም ጀምሮ በጊዚያዊ አስተዳደሩ ከነበራቸው ሃላፊነት መነሳታቸው ይገልፃል።
ፕረዚደንት ጌታቸው ረዳ ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የምስራቅ ፣ የደቡብ ፣ የማእከላይ ፣ የደቡብ ምስራቅ ፣ የሰሜናዊ ምእራብ ና የምእራብ ዞን የህዝብ ግንኙነት ፅህፈት ቤት ሃላፊ 6 ከፍተኛ አመራሮች ከስልጣን ማሰናበታቸው መዘገባችን ይታወሳል።
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከስልጣን ያነሱዋቸው ከፍተኛ አመራሮች ቁጥር የአሁኑን ጨምሮ 10 ደርሷል ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ዘግቧል።