“Let's build bridges, not walls.” Martin Luther King, Jr. — Visit my blog: https://dildiy.net/ — ድልድይ - ግላዊ እይታና ጥልቅ የመሻገሪያ እሳቤዎች የሚጋሩበት ከንባብ፣ ከኑረት እና ከምናብ የሚቀዱ ንሸጣዎች መድረክ ነው። - ሃሳቦቹ ከየትኛውም የአስተሳሰብ ጎራ (ism) አይወግኑም!! — Concern & Concept — D.S.
.
.
.
'የኔ ሁኚ' የማልልሽ የኔ በመሆን የምታጭው [የሚመስለኝን] ሁሉ ስለማስብ ነው... አብሮነትን የማልጠይቅሽ ማግስት የሚነጥቅሽ [የሚመስለኝን] ሁሉ እያብሰለሰልኩ ነው...
(የሚመስለኝ ያልኩሽ - በእኔ ልብ ውስጥ ያለውን እምነት እንጂ አንቺ ዘንድ ያለውን ጥንካሬ ስለማላውቅ ነው...)
ከልቤ እልፍኝ ያልጋበዝኩሽ ስለማልፈቅድሽ አይደለም... መንገዴን ያላጋራሁሽ ስለማልወድሽ አይደለም... ይልቁን ስለምጠነቀቅልሽ ነው... [የኔ በመሆን የምትከፍይው ዋጋ እንዳይኖር በመስጋት... ወይም በጥሬ ቃል 'ደስታዋን ስለ አብሮነታችን ሰውታ ብታዝንብኝስ?' ብዬ በመፍራት...]
[እንግዳ ነገር ይመስላል አይደል?... 'የነገን እግዜር ያውቃል' በሚል ተስፈኛ ሕዝብ መሐል በቅሎ 'ነገ ብትከፋብኝስ?' ብሎ ማሰብ ይገርማል አይደል?...]
____
[የነግ ፍርሃት እያጠየመብኝ እንጂ እኮ...]
ልብሽ ለኔ ያላትን ቦታ እረዳለሁ - [ልብሽን እንዳልሰብራት ደግሞ እፈራለሁ...]
ስታገኚኝ የፊትሽ ጸዳል ለልቤ እንዲያበራ አውቃለሁ - [የኔ አድርጌሽ ሳቅሽን እንዳልነጥቅሽ እያልኩ ግን እፈራለሁ...]
ጨዋታሽ ደዌ ሲፈውስ፣ ቃላትሽ ለነፍስ ሲደርስ፣ ፈገግታሽ መንፈስ ሲያድስ አውቃለሁ - [አብሮነታችን ስሜትሽን እንዳያጎሸው ግን ሁሌም እሰጋለሁ...]
[ግን ደግሞ ሰው አይደለሁ?...]
ዛሬ የገባኝ ሁሉ ከነፃነትሽ ላለመወለዱ፣ ዛሬ የወደድኩት ሁሉ ነገም ለመራመዱ እርግጠኝነት እንዲከበኝ እሻለሁ...
[እናም በልቤ እጠይቅሻለሁ...]
የመጣሁበት መንገድ አያዝልሽም?... የምደርስበት ነገ አያስከፋሽም?... እርጅናዬ ውስጥ ልትኖሪ ትሺያለሽ?... በጉዞዬ ልታብሪኝ በቂ አቅም አለሽ?... [ይኸውልሽ ማሬ፣ ፊቴ ላይ የማታነቢው ምሬት ከውስጤ ሊኖር ይችላል...]
ውድቀቴ ተስፋ አያስቆርጥሽም?... ድህነቴ አያስፈራሽም?... ቀርነቴስ አያሳቅቅሽም?... [ከዘመነኞችሽ ጋር ያለኝን መልከ ብዙ ልዩነትና ርቀት አውቀዋለሁ...]
ፍቅሬ ይበቃሻል?... ቤቴስ ይስብሻል?...
ህመሜን አትጠየፊውም?... ድካሜንስ አትሰቀቂውም?...
[ይሄ ሁሉ ይቅር...]
ስለ ውሳኔሽ አትጸጸቺም???...
___
ጣፋጯ...
ለነዚህ ጥያቄዎች የአዎንታ ልብ ከሌለሽ 'ና' አትበይኝ... እኔም 'ምጪልኝ' ብዬ አላስጨንቅሽም...
የወደድኩሽ የማትፈልጊውን እንድትኖሪ ከመጨከን ጋር ስላልሆነ ምርጫሽን አከብራለሁ... ግን አትርሺ - ስላላበርን ፍቅሬ ፈጽሞ አይቀየርም...
___
ይህን ግን ለምን ፃፍኩልሽ?...
ራስ ወዳድ እንዳልሆንኩ እንድታውቂ ይሆናል... [ምናልባት ደግሞ ነፃነትሽን ላስታውስሽ ብዬም ይሆናል...]
[አየሽ... ሰው በገዛ ልቡ ውስጥ ስላለች የፍቅር ኩራዝ እንጂ በሌላኛው ሰው ልብ ውስጥ ስለተዘጋጀለት እቶን መውደድ በቀላሉ እርግጠኝነት አይሰማውም... በመኖር ካልፈተነው በቀር...]
ሁሌም ግን እወድሻለሁ 💞
___
@bridgethoughts