በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
English Primer League Matchweek 16
ማንቸስተር ዩናይትድ ፣ ቼልሲ ኢና ቶተንሀም ጣፋጭ ድል ተቀዳጅተዋል !
ማንችስተር ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ያደረገውን ተጠባቂ መርሐግብር 2ለ1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
የማንችስተር ዩናይትድን የማሸነፊያ ግቦች አማድ ዲያሎ እና ብሩኖ ፈርናንዴዝ ከመረብ ሲያሳርፉ ለማንችስተር ሲቲ ቫርዲዮል አስቆጥሯል።
አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ከአሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በኋላ የመጀመሪያ የማንችስተር ደርቢ ጨዋታቸውን ያሸነፉ የመጀመሪያው የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሆነዋል።
ማንችስተር ሲቲ ካለፉት አስራ አንድ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ነው።
ቼልሲ ከብሬንትፎርድ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
የሰማያዊዎቹን የድል ግቦች ኒኮላስ ጃክሰን እና ኩኩሬላ ከመረብ አሳርፈዋል።
ቼልሲ ማሸነፉን ተከትሎ ከፕርሚየር ሊጉ መሪ ሊቨርፑል ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ማጥበብ ችለዋል።
ኢንዞ ፈርናንዴዝ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሰባት የግብ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።
ቶተንሀም ከሳውዝሀምፕተን ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
የቶተንሀምን የማሸነፊያ ግቦች ጄምስ ማዲሰን 2x ፣ ሰን ፣ ኩሉሴቭስኪ እና ፓፔ ሳር ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል።
ሰን ሁንግ ሚን በፕርሚየር ሊጉ የቶተንሀም የምንግዜም ብዙ አመቻችቶ ማቀበል የቻለችው (68) ተጨዋች መሆን ችሏል።
የሊጉ ደረጃቸው
1 ሊቨርፑል :- 36 ነጥብ
2 ቼልሲ :- 34 ነጥብ
3 አርሰናል :-30 ነጥብ
4 ኖቲንግሀም ፎረስት :- 28 ነጥብ
5 ማንችስተር ሲቲ :- 27 ነጥብ
10 ቶተንሀም :- 23 ነጥብ
12 ማንችስተር ዩናይትድ :- 22 ነጥብ
ጋዲሳ መገርሳ
ታኀሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም
ከ8ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይገኙበታል የተባለ የምክክር መድረክ በኦሮሚያ ክልል ሊጀመር ነው
ከ8ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይገኙበታል የተባለው ሀገራዊ ምክክር ነገ በኦሮሚያክልል አዳማ ከተማ ይጀመራል።
የምክክር ሂደቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዐያ ምክክሩ ከታህሳስ 7 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል ሲሉ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል።
በዚህ የምክር መድረክ ላይ 7ሺህ 20 የወረዳ የህብረተሰብ ክፍል ወኪሎች ፣3መቶ56 ወረዳዎች ፣1ሺህ 3 መቶ የክልል ባለድርሻ አካላት ፣48 ሞደሬተሮች ፣356 የክልሉ ተባባሪ አካላት፣150 በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች እንደሚሳተፉም ሰምተናል፡፡
አጀንዳው የሚቀረፅበት ዋነኛ መስፈርትም የአጀንዳው ሀገራዊ ፋይዳ ያለውና ለኢትዮጵያ ለቀጣይ ሀገረ መንግሥት ግንባታ አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆን አለበትም ተብሏል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሁን ወቅት በ9 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳዎችን ያሰባሰበ ሲሆን፤ ከነገ ታህሳስ 7 ጀምሮ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን እንደሚጀምር ተገልጿል ።
ልኡል ወልዴ
ታኀሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም
English Primer League Matchweek 16
ሊቨርፑልም እና አርሰናልም ነጥብ ጥለዋል !
የፕርሚየር ሊጉ መሪ ሊቨርፑል ከፉልሀም ጋር ያደረገውን የሊግ መርሐግብር 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቀዋል።
የፉልሀምን ግቦች ፔሬራ እና ሙኒዝ ሲያስቆጥሩ ኮዲ ጋክፖ እና ጆታ ሊቨርፑልን አቻ አድርገዋል።
አርሰናል በኤምሬትስ ስታዲየም ከኤቨርተን ጋር ያደረገውን ጨዋታ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል።
መድፈኞቹ በውድድር አመቱ ስድስተኛ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።
አርሰናል በዘንድሮው የውድድር አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ተጫውቶ ግብ ሳያስቆጥር ወጥቷል።
በሌላ ጨዋታ ኒውካስል ዩናይትድ ሌስተር ሲቲን 4ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ ኢፕስዊች ታውን ዎልቭስን 2ለ1 ረቷል።
ጋዲሳ መገርሳ
ታኀሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም
አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዋጋ ቢስ አድርገዋለች ስትል ሩሲያ ከሰሰች
የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት በአሜሪካ ምክንያት ጥቅም አልባና ደካማ እየሆነ መምጣቱን ሞስኮ አስታውቃለች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የጋዛው ጦርነት እንዳይቆም ያደረገቸው አሜሪካ ነች ብሏል።
የአለምን ሠላም ለመጠበቅ የተቋቋመው የፀጥታው ምክርቤት አሁን በአሜሪካ ምክንያት ላይ ዋጋ ቢስ እየሆነ መጥቶል ብሏል መግለጫው ።
እስራኤል በጋዛ እያደረሰች ያለችውን ጥቃት እንድታቆምና ታጋቾች እንዲፈቱ የሚደነግገውን ውሳኔ ምክርቤቱ ስድስት ጊዜ ውሳኔ አሴልፎ አሜሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ማደረጓን ሞስኮ አስታውቃለች
።
ሩሲያም በተመሳሳይ በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ስልጣኗን ተጠቅማ ውሳኔውን ውድቅ እንዳደረገች አርቲ ኒውስ ዘግቧል።
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ 45 ሺህ ዜጎች መገደላቸውንም ዘገባው አስታውሷል ።
የተኩስ አቁም እንዲደረግ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ቢወተውትም እስካሁን ማስቆም አልተቻለም።
አባቱ መረቀ
ታኀሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አፀደቀ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ 4ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ለከተማዋ ልማት ጉልህ ፋይዳ ያላቸው አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።
የጸደቁ አጀንዳዎች:-
1ኛ. የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ብክለት መከላከል ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ለከተማዋ ነዋሪዎች ጤና፣ ፅዳት እና ውበት ወሳኝ እና ጠቃሚ መሆኑን በማረጋገጥ ደንቡን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
2ኛ. በከተማ ፕላን ልማት ቢሮ የተዘጋጁና የሚዘጋጁ የአካባቢ ልማት ፕላን ዝግጀት፣ አፈፃፀም ቁጥጥር እና ደንብ ማሻሽያን መርምሮ በመወያየት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
3ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ማቅረብ በመጀመሩ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች አገልግሎት አስተዳደር ረቂቅ መነሻ ሀሳብ መርምሮ በጥልቅ በመወያየት በመንግስት እና የግል አጋርነት (PPP) እንዲተዳደሩ ብሎም በከተማዋ የመንግስት እና የግል ትራንስፖርት አገልግሎት እስከ ምሽቱ 4፡00 ድረስ ግልጋሎት እንዲሰጡ እና በሁሉም የኮሪደር ልማት በሚተገበርባቸው ቦታዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እለታዊ የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠቀሙ እንዲደረግ
4ኛ. በሁሉም የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ያሉ የንግድ እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እስከ ምሽቱ 3፡30 ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ
5ኛ. ሁሉም ዋና መንገድ እና መጋቢ መንገድ ላይ ያሉ ተቋማት፣ ህንፃዎች እንዲሁም የግልና የመንግስት ቢሮዎች ምሽት መብራት ማጥፋት እንዲከለከል እና ሙሉ የመብራት አገልግሎት እንዲኖር ውሳኔ ማሳለፉን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
ታኀሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
የነገ የታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ፕሮግራሞቻችን
Читать полностью…ዉሳኔዉ የተሻለ ነዉ ብለን እናምናለን-የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፤ መንግሥት ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባውን ነዳጅ "ለመቀነስ እየተሰራ" በመሆኑ ለአዲስ ማደያዎች ነዳጅ ላለማቅረብ መወሰኑን አስታዉቋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ጣቢያችን ያነጋገራቸዉ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር የቦርድ አባል አቶ ደሳለኝ አበባየሁ፤ በአገሪቱ ያለዉ ማደያ በአግባቡ የሚፈልገዉን ያህል አቅርቦት እያገኘ ባለመሆኑ ይህ ዉሳኔ የተሻለ ነዉ ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡
ወደ ክፍለ አገር ወጣ ሲባል በአንድ ከተማ ላይ ለከተማዉ ከሚያስፈልገዉ በላይ ማደያ ነዉ ያለዉ የሚሉት አቶ ደሳለኝ፤ በቂ የነዳጅ አቅርቦት ግን የለዉም ሲሉ ነግረዉናል፡፡
አንድ ሰዉ ከ20 እና 30 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አዉጥቶ ማደያ ገንብቶ ወደ ስራ ልግባ ቢል አቅርቦት ከሌለ ምንም ማድረግ አይችልም ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ቴክኖሎጂዉም ወደ ኤሌክትሪክ እየዞረ በቤንዚን እና ናፍጣ የሚሰሩ መኪኖች እየገቡ ባለመሆናቸዉ ፤ ዉሳኔዉ አስቀድሞ ሰዉ ሳይጎዳ በጊዜ እንዲያዉቅ ያደርገዋል ነዉ ያሉት፡፡
የነዳጅ እጥረቱን በተመለከተ ላቀረብንላቸዉ ጥያቄ፤ መንግስት የኤሌክትሪል መኪኖችን ለማስገባት በሰጠዉ አቅጣጫ መሰረት እየተንቀሳቀሰ ነዉ እኛም የምንደግፈዉ እሱን ነዉ ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
እንደ አገርም የሚጠቅመን እሱ ነዉ ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ያለውን የነዳጅ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ከውጭ ሀገር ነዳጅ የማስገባት እና ለአከፋፋይ ኩባንያዎች የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፤ ይህንን ውሳኔውን ያስታወቀው ሰኞ ሕዳር 30/2017 ዓ.ም. ለነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን በጻፈው ደብዳቤ ነው።
እሰከዳር ግርማ
ታህሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመጪው ጥር ወር መጀመሪያ እንደሚጀመር ተገለፀ
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች እያገባደደ መሆኑን ገልፆ በሚመጣው ጥር ወር መጀመሪያዎቹ እንደሚጀምር አስታውቋል።
የገበያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጥላሁን እስማኤል እንደተናገሩት ገበያው አሁን ላይ ለመጀመር ዝግጁ ነው ብለዋል።
በተለይም አቅምን ከመገንባት አኳያ እንዲሁም አክሲዎኖች ወደ ገበያው እንዲቀርቡ ከማድረግ አኳያ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉም ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ገበያው በሼሪኣ የሚተዳደሩ እና እስላሚክ የሆኑ የፋይናንስ ተቀማት በገበያው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ሰምተናል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ በአሁን ሰዓት ከአራት መቶ በላይ ሼር ሆልደሮች እንዳሉትም ተመላክቷል።
ለአለም አሰፋ
ታህሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
ብሄራዊ የጥራት ፖሊሲን ማፅደቅ ጥራትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርአት እንዲኖር ያደርጋል ተባለ።
ይህ የጥራት ፖሊሲ የሚመረቱ ምርቶች ለኅብረተሰቡ እንዲውሉ የሚያስችል እና ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ተወዳዳሪ የሚያደርግ ሁኔታን የሚፈጥር ነዉ ተብሏል።
የብሄራዊ ጥራት ፖሊሲ ረቂቅ መዘጋጀቱን ከዚህ ቀደም ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር መግለፁ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጀት የገበያ ልማት እና የኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተክኢ ብርሃን ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ "ይህ የጥራት ፖሊሲ መኖር ማንኛውም አገልግሎት ሰጪ ÷ ላኪ እና አስመጪ በአንድ ቋንቋ መናገር የሚያስችለዉ ህግ ነዉ" ብለዋል።
የዚህ ፖሊሲ መፅደቅ ከአለምአቀፍ ገበያ እና የኢኮኖሚ ማእቀፎች ጋር ለመጣጣም የጥራት ፖሊሲዉ ወሳኝነት ሚናዉ የጎላ ነዉ ሲሉ ገልፀዋል።
የግብይት መስፈርቶች የአለም አቀፍ አሰራር ስርአቶች በማካተት የተዘጋጀዉ ፖሊሲ እንደሆነም የኮምኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በዚህም ብሄራዊ የጥራት ፖሊሲን ማፅደቅ ጥራትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርአት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል
ዳይሬክተሩ አያይዘዉም ምርትን፣ አገልግሎትን ወይም የሥራ አመራር ሥርዓትን የሚመለከቱ ደረጃዎችና ሕጋዊ መስፈርቶች መሟላታቸውን የማረጋገጥ ሃላፊነት ያለዉ የተስማሚነት ምዘና በአለም ንግድ ዉስጥ ተቀባይነት እንዲኖር እየሰራ ነዉ ብለዋል
ተቋሙ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 6,823 የአገልግሎት ጥያቄዎችን በማስተናገድ የጥራት ማረጋገጥ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልፆል።
ቁምነገር አየለ
ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
በህገወጦች ምክንያት ከስራ ወጥተው የነበሩ ነጋዴዎች ወደ ስራ መመለሳቸዉ ተነገረ
በህገወጦች ምክንያት ከስራ ወጥተው የነበሩ ነጋዴዎች በተሰሩ ስራዎች ወደ ንግድ ስርአቱ መመለሳቸውን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታቋል።
ግብይቶችን በደረሰኝ እንዲከውኑ ለማደረግ በተሰራ ስራ በህገወጦች ምክንያት ከስራ ወጥተው የነበሩ ነጋዴዎች ወደ ንግድ ሰረአቱ መመለሳቸውን ቢሮው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጿል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለጣቢያችን እነደተናገሩት በመርካቶ እና አካባቢው የንግድ እና የግብይት ስርአቱ በህጋዊ መንገድ ለማስኬድ የክትትል እና የቁጥጥር ሰራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
በከተማው ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ የሚመራ ግብረ ሀይል በማቐቐም ገቢዎች ቢሮ ፤ ንግድ ቢሮ ፤ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ፍትህ ቢሮን በማቀናጀት እየተሰራ መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ተናግረዋል ።
በከተማው ከ 6 ሺህ በላይ ነጋዴዎች የተገኙበት ከተማ አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መካሄዱንም አስታውሰዋል ።
አቤል እስጢፋኖስ
ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
ዩክሬን በምዕራባዉያን እንደተከዳች ስሎቫኪያ አስታወቀች
ዩክሬንን ሲደግፏት የነበሩ የምዕራቡ አለም አገሮች ግዛቶቿን አሳልፈዉ በመስጠት ክህደት እንደሚፈፅሙባት የስሎቫኪያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ ዩክሬን አንድ ሶስተኛ የሚሆነዉን ግዛቷን እንደምታጣም ገልፀዋል፡፡
ምዕራባዉያን ሩሲያን እናዳክማለን በሚል ሲሴሩት የነበረዉ ሴራ መክሸፉንም አንስተዋል፡፡
ስሎቫኪያ ምንም እንኳን የኔቶና የአዉሮፓ ህብረት አባል አገር ብትሆንም ፊኮ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ግን ገለልተኛ አቋም እያራመዱ ነዉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሩሲያ ጋር በሰላም መኖር እንደሚፈልጉም አስረድተዋል፡፡
አባቱ መረቀ
ታኀሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚውን አውቀ::
በ2018 ዓ.ም ነሀሴ ወር ላይ በፖላንድ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ድልድል ይፋ ሆኗል።
በድልድሉ የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከኬንያ አቻው ጋር ተደልድሏል።
የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በቀጣዩ ዓመት መስከረም ወር ላይ ይደረጋሉ።
የኢትዮጵያ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የኬንያ አቻውን በደርሶ መልስ ማሸነፍ ከቻለ በሶስተኛው ዙር ማጣሪያ ከታንዛኒያ እና አንጎላ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
በ2024 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻው ዙር ማጣሪያ በሞሮኮ አቻው ተሸንፎ ወደ ውድድሩ ማለፍ ሳይችል መቅረቱ ይታወሳል።
በ 2018 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ድልድል ይፋ ሆኗል።
በድልድሉ በቋት ሁለት የተመደበው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከዚምባቡዌ አቻው ጋር ተደልድሏል።
በዚምባብዌ የሚደረገው የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ቀዳሚ ጨዋታ ከጥር 2 እስከ ጥር 5 ባሉት ቀናት መካከል ሲደረግ በኢትዮጵያ የሚደረገው የመልስ ጨዋታ ደግሞ ከሳምንት በኋላ ከጥር 9 እስከ ጥር 12 ባሉት ቀናቶች መካከል ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የዚምባቡዌ አቻውን በደርሶ መልስ ማሸነፍ ከቻለ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ከግብፅ እና ካሜሩን አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
ጋዲሳ መገርሳ
ታኀሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
የነገ የታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ፕሮግራሞቻችን
Читать полностью…የተጋነኑ ማስታወቂያዎችን በሚሰሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለፀ።
የተጋነኑ ማስታወቂያዎችን የሚሰሩ አካላት ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች መኖራቸዉንና በህግና ስርአት ማስታወቂያቸዉ እንዲታገድ መደረጉን ሰምተናል።
ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የዋና ዳይሬክተር ፅ/ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ዮናስ ፋንታዬ ፤ ምርቱ እንዳለ አድርገዉ የሚያስተዋዉቁ እንዳሉና ማህበረሰቡ ምርቱን ለመግዛት ቦታዉ ሲሄድ ግን ብዙ ጊዜ ምርቱ እንደማይኖር ተናግረዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር ተግባራዊ ባደረገው አዋጅ መሰረት ብቁ የሆኑ ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች ስራቸዉን መስራት እንደሚችሉ አንስተዉ በየጊዜዉ ግን የቁጥጥር ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡
ነገር ግን በህግ ጥበቃ ያገኙ መብቶችን የሚጥሱ፤ ወይም የሰዎችን ማንነት እና ክብር የሚጎዱ ማስታወቂያዎችን ተቋማት ከማሰራጨት መቆጠብ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ፍትህ ሚኒስቴር በህገ መንግስቱ የተደነገጉ የእኩልነት ድንጋጌዎችን በመጻረር የእኩልነት መርህን በሚጥስ መልኩ ማስታወቂያን ማሰራጨት በህግ የተከለከለ ስለመሆኑ ደንግጓል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲሱ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ቃለ መሀላ ፈጸሙ፡፡
አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሒ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሆነው ዛሬ ሐሙስ ቃለ መሀላ ፈጸሙ።
ኢሮ በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የተቃዋሚው ዋዳኒ ፓርቲ መሪ የራስ ገዟ ሶማሌላንድ 6ኛ ፕሬዝደንት ሆነዋል።
የ69 ዓመቱ አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሒ ከዚህ ቀደም የሶማሌላንድ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የነበሩ ናቸው።
ሶማሊላንድ በ እ.ኤ.አ. 1991 ዓ.ም. ነው በተናጠል በወሰደችው ውሳኔ ከሶማሊያ ተለይታ እራስ ገዝነቷን ያወጀችው። እስካሁን ዓለም አቀፍ እውቅና አላገኘችም።
ሆኖም ምርጫውን ለመታዘብ በመላው ሶማሊላንድ ግዛት 28 ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ተሰማርተው እንደነበር አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል።
ታህሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተበድረዉ መክፈል ያልቻሉት ዕዳ ወደ ህዝብ የሚዞር ነዉ - የፋይናንስ ባለሙያ እና ተንታኝ ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ
የመንግስት የልማት ድርጅቶች እንደ ማንኛዉም የንግድ ተቋም ያለ መንግስት በጀት የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም ፤ ተበድረዉ መክፈል ያልቻሉት ዕዳ ግን ወደ መንግስት እና ህዝብ የሚዞር ነዉ ሲሉ ነግረዉናል፡፡
እነዚህ የልማት ድርጅቶች የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ ያልቻሉበትን ምክንያቶች የሚዘረዝሩት ባለሙያዉ ፤ የአመራር ብቃት ማነስ፣በዉጭ ምንዛሪ እና ከአገር ዉስጥ ባንኮች የተወሰዱ ከፍተኛ ወለድ ያላቸዉ ብድሮች ብድራቸዉን መመለስ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ነዉ የሚሉት፡፡
የዉጭ ምንዛሪ ብድር መዉሰዳቸዉ የብር የመግዛት አቅም እየወረደ ሲመጣ የዕዳ መጠን እንዲጨምር በማድረግ ተቋማቱ ከፍተኛ ዕዳ ዉስጥ እንዲዘፈቁ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
እነዚህ የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረዉ መክፈል ያልቻሉትን ገንዘብ ባንኩ ድርጅቶቹን ሳይሆን መንግስትን ነዉ የሚጠይቀዉ ሲሉ ነግረዉናል፡፡
መንግስት ይህንን ገንዘብ የመክፈል ግዴታ ከድርጅቶቹ ላይ ቢያነሳም፤ አሁንም ቢሆን ድርጅቶቹ አትራፊ ይሆናሉ የሚል እምነት ግን የለኝም ብለዋል ዶ/ር አብዱልመናን፡፡
እነዚህ ድርጅቶች አሁንም ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ያሉ ናቸዉ የሚሉት ባለሙያዉ ፤ ወደ ፊት አትራፊ ይሆናሉ የሚለዉ ጉዳይ ያጠራጥረኛል ብለዋል፡፡
መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ስምንት የልማት ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር እንዲተዳደሩ መወሰኑ የሚታወስ ነዉ፡፡
እስከዳር ግርማ
ታኀሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም
ቡና ባንክ 9መቶ 30 ሚሊየን ብር ትርፍ አስመዝግቤያለሁ አለ።
ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ትርፉ በ4መቶ29 ሚሊየን ብር ቅናሽ ማሳየቱንም ባንኩ አስታውቋል።
በበጀት አመቱ እንደ አገር የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ፣ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ፣ ተደራራቢ የሆኑ የተቆጣጣሪ አካላት መመሪያዎች መውጣት እንዲሁም ተግባራዊ መሆን ለባንኩ ዘርፍ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደነበር ተገልጿል።
የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር አለማየሁ ሰዋገኝ፤ እነዚህ ችግሮች የባንኮችን የማበደር ብቻ ሳይሆን ተቀማጭ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ላይም ተፅዕኖ ማሳደራቸውን ተናግረዋል።
ነገርግን ባንኩ ላስመዘገበው የሀብት ዕድገት የተሰጡ የብድር አቅርቦቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙም ገልጸዋል።
በዚህም የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ8.14 ቢሊየን ብር ዕድገት በማሳየት 54.53 ቢሊየን ብር መድረሱን አስታውቀዋል።
በበጀት አመቱ የተመዘገበው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ549.2 ሚሊየን ብር ጭማሪ በማሳየት ወደ ብር 4.83 ቢሊየን ማደግ ችሏል ነው የተባለው።
ባንኩ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የካፒታል መጠን እንዲሁም የተከፈለ ካፒታል መጠን ከተቀመጠው ጊዜ ቀደም ብሎ ለማሟላት ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።
ከዕቅዱ አንፃር ዝቅ ያለ ቢሆንም 4መቶ90 ሚሊየን 1መቶ16 ሺህ ብር ለባንኩ ባለአክሲዮኖች በትርፍ ክፍያ እንዲከፋፈል ውሳኔ መደረሱንም ገልፀዋል።
ባንኩ በያዝነው በጀት አመት ሩብ አመት መጀመሪያ ላይ ከዕቅዱ በላይ 1.2 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱንም ሰምተናል።
ቡና ባንክ የባለአክሲዮኖች 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።
እስከዳር ግርማ
ታኀሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር በረራውን አቋረጠ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሰላም ማረፍ መቻሉን አሳውቋል።
የበረራ ቁጥሩ ET 612 የሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ታህሳስ 05 ቀን 2017 ዓ.ም፥ ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ በሚያደርገው በረራ ከተነሳ ከ30 ደቂቃ በኋላ የቴክኒክ ችግር ስላጋጠመው ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሰላም ማረፍ መቻሉን አሳውቋል።
ለጥንቃቄ ሲባልም መንገዶኞች እና የበረራ ሠራተኞች በአስቸኳይ ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ተደርጓል ሲልም አየር መንገዱ በመግለጫው አስታውቋል።
በዚህ አጋጣሚ መንገደኞች ለደረሰባቸው መጉላላት አየር መንገዱ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን፥ የቴክኒክ ችግሩ በመጣራት ላይ መሆኑንም ገልጿል።
ታኀሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም
የእስራኤል ወታደሮች በሶሪያ መዲና ቅርብ ርቀት ላይ መድረሳቸው ተነገረ
የበሽር አላሳድ መንግስት መውደቁን ተከትሎ ጦሯን ወደ ሶሪያ ያዘመተችው እስራኤል ወታደሮቿ በደማስቆ ቅርብ ርቀት ላይ መስፈራቸው ታውቋል።
ወታደሮቹ የደማስቆን መግቢያ እንተቆጣጠሩና ወደ ከተማዋ ለመግባት 20 ኪሎ ሜትር ብቻ ቀርቷቸዋል።
የእስራኤል ጦር የበሽር አላሳድ ወታደሮች ጥለዋቸው የሸሹትን የጦር መሳሪያዎች እየተቆጣጠረ እንደሚገኝም እየሩሳሌም ፖስት አስነብቧል።
የአላሳድ መንግስት መውደቁን ተከትሎ አደገኛ የጦር መሳሪያዎች በአማፅያኑ እጅ ይገባሉ በሚል ስጋት ቴልአቪቭ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየወሰደች ትገኛለች።
በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነትም በፍረሱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው።
እስራኤል ሶሪያው መውረሯን ተከትሎ አክቸኳይ ስብሰባ የተቀመጠው የአረብ ሊግ ድርጊቱን አውግዟል።
አባቱ መረቀ
ታኀሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም
ትራምፕ ኢራንን ለመምታት ከእስራኤል ጋር እየመከሩ ነዉ ተባለ
ተመራጩ የአሜሪካዉ ቀጣይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተመንግስት ከገቡ በኋላ ለእስራኤል ወግነዉ ኢራንን የመምታት ፍላጎት አላቸዉ ተብሏል፡፡
ትራምፕ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስተር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስልክ ደዉለዉ ኢራን ፈፅሞ ኒዉክሌር መታጠቅ የለባትም ሲሉ ነግረዋቸዋል ፡፡
እናም ከእስራኤል ጋር በማበር የኢራንን የኒዉክሌር ጣቢያዎች የመምታት ፍላጎት እንዳላቸዉ ዎል ስትሬት ጆርናል ከምንጮች አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ይሁን እንጅ የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካን ግልፅ የሆነ ጦርነት ዉስጥ የመክተት ፍላጎት እንደሌለዉ ሪፖርቱ አንስቷል፡፡
ዶናልድ ትራም በመጀመሪያዉ የስልጣን ዘመናቸዉ አገራቸዉን ከ2015ቱ የኒዉክኬር ስምምነት በማግለል ኢራን ላይ ከባባድ ማዕቀቦችን ሲያዘንቡ እንደነበር የሚታወሰ ነዉ፡፡
ታህሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
በቬኔዙዌላው ምርጫ ሂደት የተያዙ ከመቶ በላይ እስረኞች መለቀቃቸዉ ተገለፀ
ቬንዙዌላ በሃምሌ ወር አድርጋዉ በነበረዉ አወዛጋቢ ኘሬዝዳንታዊ ምርጫ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ምርጫዉን ማሸነፋቸዉ የሚታወስ ነዉ።
የሀገሪቱ የዜጎች ደህንነት አገልግሎት ትናንት በሰጠዉ መግለጫ ከማክሰኞ እስከ ሀሙስ በነበረዉ ጊዜ እስረኞችን ለመፍታት ተችሏል ሲል አስታውቋል።
በዚህ ምርጫ ሂደት ዉስጥ ተቃዋሚዎች ለእስር የተዳረጉበት ሲሆን እነዚህ 103 ያህል እስረኞች 72 ሰአታት ዉስጥ መለቀቃቸውን እየተነገረ ነዉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሌሎች ተጨማሪ 225 እስረኞች ለመፍታት ፍቃድ ቢሰጥም በወር አንድ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረብ ግዴታ የተጣለባቸዉ መሆኑን የጠቅላይ አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት ገልፆል።
በምርጫዉ ሂደት ዉስጥ የተፈፀመው ወንጀሎች እና የአመፅ ተግባራትን መንግስት እንዲገመገም ትእዛዝ ተላልፏል።
ፕሬዝዳንት ማዱሮን ሀገሪቱን ለ 11 አመታት የመሩ ሲሆን በዚህኛው ምርጫ ስለማሸነፋቸዉ ማረጋገጫ አልቀረበልንም ሲሉ ተቃዋሚዎች ገልፀዋል ዘገባዉ የአልጀዚራ ነዉ።
ቁምነገር አየለ
ታህሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ያለ ህግ አግባብ የታሰሩ ኤርትራውያን እንደሌሉ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።
መስሪያ ቤቱ በርካታ ኤርትራውያን በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በመቆየት ለውጭ አገር ዜጎች ባልተፈቀዱ የስራ መስኮችን ጨምሮ በኮንትሮባንድ፣ በህገወጥ ሰው ዝውውር እና በሌሎች ህገወጥ ተግባሮች ተሰማርተው የሚገኙ እንዳሉ ጠቅሶ እነዚህ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጿል።
በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በኤርትራውያን ላይ የጅምላ እስራት እየተካሄደ እንደሆነ ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው በርካታ በከተማዋ የሚኖሩ ኤርትራውያን ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ከሃገር ማባረርም ሆነ እስር እንዳልተፈጸመ ገልጾ ነገር ግን "የሃገርን ብሔራዊ ደህንነትና ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ህገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች" ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ አሳስቧል።
በህገወጥ መንገድ ወደ አገር የገቡ ኤርትራውያንን መስሪያ ቤቱ ወደ ህጋዊ መንገድ ለማስገባት በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም የተመዘገቡት ውስን ናቸው ብሏል።
ሆኖም ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድና የስራ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ በሃሰተኛ ማንነት ለውጭ አገር ዜጎች ባልተፈቀዱ የስራ መስኮች ከትንሽ ሱቅ ችርቻሮ እስከ ትላልቅ ስራዎች በህገወጥ መንገድ ተሰማርተው እንደሚገኙ አጽንኦት ሰጥቷል።
ታህሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
በሽር አላሳድ በዩክሬን ጦርነት የተጎዳችዉን ከተማ መጠገን ይኖርባቸዋል ተባለ
ከስልጣን የተወገዱት የሶሪያዉ ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ በሩሲያ መኖር ከፈለጉ በዩክሬን ጦርነት የወደመችዉን የማሪዮፖል ከተማን መልሶ ለመገንባት የሚደረገዉን ጥረት መደገፍ አለባቸዉ ተብለዋል፡፡
የሩሲያ የፓርላማ አባል የሆኑት ዲሚትሪ ኩዝኔስቶቭ አሳድን ወደ ዶንባሷ ማሪዮፖል መላክ ለእርሳቸዉም ለቤተሰባቸዉን ጥሩ ነዉ ብለዋል፡፡
በሽር አላሳድ አሁን ላይ ሞስኮ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጅ የማሪዮፖል ከተማን መልሶ ለመገንባት አሳድም አስተዋፅኦ ማድረግ ይኖረባቸዋል መባሉን አርቲ ዘግቧል፡፡
አባቱ መረቀ
ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሊሆን የማይገባውን “ የዘር ማጥፋት ዘመቻን የሚደግፉ የሶስተኛ ወገን ሀገራት አሉ ተባለ
የኮሎምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊስ ጊልቤርቶ ሙሪሎ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈፅሞ መሆን የሌለበትን የዘር ማጥፋት ዘመቻን በግልጽ የሚደግፉ የሶስተኛ ወገን ሀገራት አሉ ብለዋል።
ሙሪሎ በዶሃ የውይይት መድረክ ላይ በጋዛ ስላለው ችግር ለሃገራት መሪዎችን ተችተዋል ።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተባባሰ የመጣውን የጋዛ ብጥብጥ መፍታት አለመቻሉ ያሳዝናል ያሉት ሚሲትሩ ይህ ተግባር 'የዘር ማጥፋት ወንጀል' ነው ሲሉም ነቅፈዋል።
ይሁን እና ሚኒስትሩ በጋዛ ያለውን ሁኔታ በግልፅ እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራትን ጨምሮ ሌሎች የዘር ማጥፋት ዘመቻውን የሚደግፉት የሶስተኛ ወገን ሀገራት መንግስታት ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
ልዑል ወልዴ
ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
ትረምፕ ሩሲያን በረጅም ርቀት ሚሳኤል ማስመታት ሞኝነት ነዉ አሉ
ተመራጩ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምዕራባዉያን ዩክሬን ሩሲያን እንድትመታ መፍቀዳቸዉ ስህተት ነዉ ብለዋል፡፡
ዩክሬን የአሜሪካ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ተጠቅማ ሩሲያን መምታቷን ተከትሎ ነዉ ትራምፕ ሁኔታዉ ያሳስበናል ሲሉ የተናገሩት፡፡
የፕሬዝዳንት ጆ ባይይንና የዜሌንስኪ ዉሳኔ ግጭትን የሚያባብስ የሞኝ ዉሳኔ ነዉ ሲሉ አጣጥለዉታል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ይህንን የተናገሩት የክሪሚሊኑ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሞስኮ የመልስ ምት ትሰጣለች ማለታቸዉን ተከትሎ ነዉ፡፡
ዩክሬን የአሜሪካን ሚሳኤል ተጠቅማ ደቡባዊ ሩሲያን መምታቷን አርቲ ኒዉስ አስታዉሷል፡፡
አባቱ መረቀ
ታኀሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
ሩሲያ ዜጎቿ ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ አስጠነቀቀች
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎች ወደ አሜሪካ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ ማሪያ ዛካሮቫ በሰጡት መግለጫ ዜጎቻችን በአሜሪካ ለተያዩ ጥቃቶች እየተዳረጉ ነው ብለዋል ።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት በእጅጉን እየሻከረ በመምጣቱ የሩሲያ ዜጎች ወደ አሜሪካ መሄድ እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።
ማሪያ ዛካሮቫ ዜጎች ወደ አሜሪካ ሲያቀኑ ለዕስርና እንግልት እየተዳረጉ እንደሆነም አንስተዋል ።
አሜሪካና ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሚገኙ አርቲ ኒውስ ዘግቧል።
ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
የሶማሊያ መከላከያ ሰራዊት የጁባላንድ ከፊል ራስ ገዝ ክልልን ለቆ ወጣ ።
በሶማሊያ መከላከያ ሰራዊት እና በጁባላንድ ከፊል ራስ ገዝ ኃይሎች መካከል ትናንት ረቡዕ ከተቀሰቀሰ ዉጊያ በኋላ የሶማሊያ መከላከያ ግዛቲቱን ለቆ መውጣቱን የሞቃዲሾ መንግስት ዛሬ አስታውቋል።
የመንግስት እና ወታደራዊ ባለስልጣናት በራስ ካምቦኒ ከተማ እና አካባቢው ለበርካታ ሰዓታት ለቆየው ዉጊያ አህመድ ማዶቤ የሚመሩት የከፊል ራስ ገዟ አስተዳደር ጦር ትናንት ረቡዕ ግጭት ቀስቅሷል በማለት ከሰዋል።
ባለስልጣናቱ "የሶማሌ ብሄራዊ ሃይሎች ከጂሃዲስቶች ጋር እንጂ ከሌላ ከማንም ጋር የትጥቅ ትግል የማድረግ መመሪያ አልተሰጣቸዉም።" ብለዋል።
የጁባላንድ ባለስልጣናት ትናንት ረቡዕ ግጭቱ ሲቀሰቀስ ባወጡት መግለጫ የፌዴራል ኃይሎች በድሮን የታገዘ ጥቃት ፈጽመውብናል ሲሉ ለግጭቱ መቀስቀስ የፌዴራል መንግስቱን ተጠያቂ አድርገዋል።
ከጁባ ላንድ ዛሬ የተሰማው ዜና ግን ከዉግያው በኋላ የፌዴራል ኃይሎች ጁባ ላንድን ለቀው መውጣታቸውን ነው የሚያመለክተው።
የጁባ ላንድ ባለስልጣናት ይህንኑ በሚያረጋግጠው መግለጫቸው « የጦር ሰፈሩን መልሰን ተቆጣጥረናል» ፤ ብለዋል። የአካባቢው የፀጥታ ጥበቃ ምክትል ሚኒስትር አዳነ አህመድ«በመጨረሻም የጁባላንድ ወታደሮች ከቀትር በኋላ የራስ ካምቦኒ ከተማ ተቆጣጥረውታል» ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በአንድ ቀን ዉግያው ከሁለቱም ወገኖች የተገደሉ ወታደሮች መኖራቸውን ያመለከተው የሮይተርስ ዘገባ ነገር ግን አኃዙን በተመለከተ መረጃ አለማግኘቱን ጠቅሷል።
ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
ትራምፕ የቻይናዉ ፕሬዝዳንት ለበዓለ ሲመታቸዉ እንዲገኙ ጥሪ አቀረቡ
በቀጣዪ ወር ወደ ነጩ ቤተመንግስት ገብተዉ አሜሪካን ማስተዳደር የሚጀምሩት ዶናልድ ትራምፕ የቻይናዉ ፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ በበዓለ ሲመታቸዉ ላይ እንዲገኙ ጋብዘዋቸዋል፡፡
ትራምፕ ከሺ ጂፒንግ ጋር በቅርብ ሳምንታት ዉስጥ መወያየታቸዉንም አስታዉቀዋል፡፡
የቻይናዉ ፕሬዝዳንት ስለ ግብዣዉ ያሉት እንደሌለ የዘገበዉ አርቲ ኒዉስ በበዓለ ሲመቱ ላይ ይገኙ አይገኙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
ከዚህ ቀደም አንድም የቻይና ፕሬዝዳንት በአሜሪካ አቻቸዉ በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተዉ አያዉቁም፡፡
በሌላ በኩል ዶናልድ ትራምፕ ለሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የግብዣ ጥሪ እንዳለደረጉ ክሪሚሊን አስታዉቋል፡፡
አባቱ መረቀ
ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
የምንዛሪ ተመኑ ከባንክ ጋር ከ3 እስከ 5 ብር ልዩነት እንዳለው ሮበስት የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ገለፀ።
በቅርቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ ፍቃድ ከተሰጣቸው 5 ቢሮዎች አንዱ ነው።
የ ሮበስት ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌቱ ሙሊሳ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የምንዛሪ ተመኑ ከዕለት ዕለት ቢለያይም ከባንክ አንፃር ከ3 እስከ 5 ብር ልዩነት እንዳለው ነግረውናል።
ይህን የውጭ ምንዛሪ ቢሮ በኤርፖርት ውስጥ ለመክፈት ዕቅድ እንዳለ ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ፤ አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ውጭ በመቀሌ ቅርንጫፍ መከፈቱን ተናግረዋል።
የመቀሌው ቅርንጫፍ ስራ ከጀመረ ሶስት ሳምንት አከባቢ መሆኑንም አንስተዋል።
የውጭ ምንዛሪ ይገኝባቸዋል ተብሎ በሚታሰቡ አከባቢዎች ላይ ቢሮዎችን እንደሚከፍቱ የነገሩን አቶ ጌቱ፤ መቀሌ የተመረጠችው ከወርቅ ንግድ ጋር ተያይዞ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመቀሌ በተጨማሪ በአዳማ እና ድሬዳዋ ቅርንጫፎችን ለመክፈት መታቀዱንም ነው የነገሩን።
ቢሮው ያለ ጉምሩክ ፍቃድ እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መግዛት የሚችል ሲሆን፤ የጉምሩክ ፍቃድ በሚያቀርቡት ጊዜ ደግሞ ከዛ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት ይችላል።
ቱሪስቶች 5 ሺህ እና የቢዝነስ ተጓዦች ደግሞ ያለ ጉምሩክ ማዘዣ እስከ 10 ሺህ ብር ከቢሮው መግዛት እንደሚችሉም አንስተዋል።
በተጨማሪም ለአስመጪ እና ላኪ ድርጅቶች LC መክፈትን ጨምሮ ለግል ተጓዦች እስከ 5 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ ለመሸጥ በብሔራዊ ባንክ ፍቃድ አግኝተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የግል ድርጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ መስጠት መጀመራቸው ይታወቃል።
እሰከዳር ግርማ
ታህሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም