በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
ተመድ በሱዳን ያለው ጦርነት መባባስ በሀገሪቱ መጠነ ሰፊ ረሀብ እንዲታይ እያደረገ ነው ሲል አስጠንቅቋል።
በሀገሪቱ 24.6 ሚሊየን ዜጎች ለከፍተኛ ረሃብ ተዳርገዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተናግሯል።
የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ በሱዳን በሁለቱ የጦር ሀይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የተጠጋዉ ግጭት ሀገሪቷን ወደ ገሀነም ቀይሮታል ሲል ነዉ የገለፀዉ ።
ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቶች እየታዩ ቢሆንም የእርዳታ ድርጅቶች በጦርነቱ ሳቢያ ስራቸዉን ስለማቋማቸዉ ጠቅሷል።
ከሰሞኑ ከግማሽ ሚሊዩን በላይ የተፈናቃይ ቁጥር ባለዉ የዘምዘም ካምኘ እርዳታ እየሰጠ የነበረዉ የድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በግጭቱ መባባስ ምክንያት በካምፑ እየሰጠ የነበረዉ እርዳታ ለማቆም መገደዱን አሳዉቋል።
የሱዳንን ድንበር ጥሰው የተሰደዱትን 3.4 ሚሊዮን ጨምሮ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸዉን ሪፓርቱ ጠቁሟል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት እና ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ህጻናት ከመደበኛ ትምህርት አቋርጠዋል ብሏል።
በተጨማሪም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በካምፑ የምግብ እርዳታ መቋረጡን በጸጥታ ሁኔታ ምክንያት እንደሆነ ማረጋገጡን ተገልፆል።
የፀጥታው ምክር ቤት ሁሉም ተዋናዮች በአለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋት እንዲያከብሩ እየጠየቀ ቢገኝም የጦር ወንጀል ግድያዎችን ስለመኖራቸዉ ሪፖርቶች አረጋግጠዋል ብሏል።
የሱዳኑ አምባሳደር አል ሀሪዝ ኢድሪስ መንግስታቸው ሰብዓዊ ርዳታዎችን ለማመቻቸት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠው ሀገሪቱ የወደፊት ፖለቲካዋን ለመፍታት እየሰራች መሆኑን እየገለፁ ይገኛል ሲል አፍሪካ ኒዉስ ዘግቧል።
ቁምነገር አየለ
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዶ/ር ለይፋዊ ጉብኝት ሶማሊያ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሞቃዲሾ አዳን አብዱል አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የሶማሊያ የዜና ምነጮች ዘግበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት ውጥረት ለማርገብ ከተስማሙ ወዲህ ሞቃዲሾ ሲገቡ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በቆይታቸውም ከፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ሶማሊያ እንደ ግዛቷ አካል ከምትቆጥራት ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማሻከሩ ይታወሳል።
ከአንድ አመት በላይ የዘለቀው ውጥረት በቱርክ አደራዳሪነት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በአንካራ ፊትለፊት ከተገናኙ በኋላ መርገቡም አይዘነጋም።
በአንካራው ስምምነት መሰረትም የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት ባለፉት ወራት በሞቃዲሾ እና በአዲስ አበባ በመገናኘት ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሞቃዲሾ ጉብኝትም የእስካሁኑን ንግግር ለማጽናት ያለመ እንደሚሆን ተዘግቧል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በጥር ወር መጀመሪያ በአዲስ አበባ የሁለት ቀናት ጉብኝት ሲያደርጉም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው።
በቱርክ አቀራራቢነት የተደረሰው ስምምነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከሶማሊያ የሉዓላዊነት ስጋቶች ጋር በማጣጣም አዲስ አበባ የሶማሊያ ወደቦችን እንድትጠቀም እንደሚያስችል ተነግሮ ነበር።
ሀገራቱ ውጥረት ውስጥ በነበሩበት ወቅት አነጋጋሪ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደሮች የሶማሊያ ቆይታ ጉዳይም ስምምነት ተደርሶበታል።
ሀገራቱ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው መገለጹ አይዘነጋም።
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚደርሰው ዝርፊያ እና ውድመት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የኢትዮጵያኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳወቀ፡፡
በአጥፊዎች ላይ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ እየተወሰደ ባለመሆኑ የስርቆት ወንጀሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል ሲል በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
ከሰሞኑ በአምቦ፣ ደሴ፣ ጎንደርና ወልድያ ሪጅኖች ላይ በተፈፀመ ስርቆት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንቦኞችን ከማጉላላቱም ባሻገር ከ16 ሚሊዮን 8 መቶ 60 ሺ ብር በላይ የሚገመት የንብረት ጉዳት መድረሱን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
በዚህም በአምቦ ሪጅን ብቻ 8 የተለያየ አቅም ያላቸው የዲስትሪቡሽን ትራንስፎርመሮች፤ በወልድያ፣ ጎንደርና ደሴ ከ5 በላይ ከፍተኛ የኤሌክተትሪክ አስተላላፊ መስመር ተሸካሚ ታወሮች ላይ ስርቆት ተፈፅሟል፡፡
በአጥፊዎች ላይ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ እየተወሰደ ባለመሆኑ የስርቆት ወንጀሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል ሲል በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተቋሙ በተለያዩ ጊዚያት የዲስትሪቡሽን ትራንስፎርመሮች፣የኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮችና ታወሮች ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች ዝርፊያና ውድመት እየተፈፀመ በመሆኑ የኤሌክትሪክ የተደራሽነትን ማስፋት በሚያደርገው ጥረት ላይ ተግዳሮት እየሆነ እንደመጣበት ተናግሯል፡፡
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
ዩክሬን ኔቶን ለመቀላቀል ያላትን ፍላጎት ትርሳው አሉ ትራምፕ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በነገው እለት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ይገናኛሉ፡፡
የዩክሬኑ ዜለንስኪ ፤ አሁንም ቢሆን የሩስያ ጥቃትን ለመከላከል የአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤት ዋስትና እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ነገር ግን ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ በኋላ ለዩክሬን ዋስትና እንደማትሰጥ ተናግረው፣ ኃላፊነቱ በአውሮፓ ላይ መውደቅ አለበት ብለዋል፡፡
ትራምፕ ዩክሬን የኔቶ አባል የመሆን ሀሳቧን እንድትተው የገፁም ሲሆን ለጦርነቱ መንስኤ የሆነውን ጉዳይ ፈፅሞ ማሳብ እንደሌለባት አስታውቀዋል፡፡
ይህ ብቻም አይደል ትራምፕ ከኔቶ አባልነት አሜሪካ እንደምትወጣ መጠቆማቸውን ተከትሎ ጉዳዩ የአውሮፓ ሀገራት ማሳሰቡን ቀጥሏል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የውልሰው ገዝሙ
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
በማይናማር እና በታይላንድ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጲያውያ ስደተኞች ከፍተኛ ስጋት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በማይናማር 7ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በተለያዩ ካምፓች ታግተው ይገኛሉ፡፡
በተለያዩ የውጪ የስራ ዕድሎች ተታለዉ በማይናማር እና በታይላንድ ካምፓች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡
በተለይ ከማይናማር ወደ ታይላንድ ገበተው ፤ ከታይላንድ ወደ ሃገራቸዉ መመለስ የሚፈልጉ ዜጎች መንግስት ይድረስልን ሲሉ ለጣቢያችን ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡
እነዚህ ኢትዮጲያውያን፤ በማይናማር እና በታይላንድ ከተያዙበት ካምፕ እስካሁን ባለመውጣታቸው ምክንያት ለተጨማሪ ጉዳቶች እየተዳረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
እስካሁን ከማይናማር ወደ ታይላድ የተለቀቁት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ብዛት 138 እንደሆነ ያረጋገጠው በሕንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ በበኩሉ አስፈላጊው ሰነድ ተሟልቶላቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ መገለፁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ከእነዚህ ካምፖች ለማስወጣት ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ከማይናማር መንግሥት ጋር ንግግር እያደረገ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር።
ያነጋገርናቸዉ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደገለፁት አሁንም ቢሆን ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት ወደ ሀገራችዉ እንዲመለሱ እየተደረገ አይደለም ብለዋል።
ጣቢያችን ይህንን ቅሬታ ይዞ የሚመለከተዉን የውጪ ጉዳይ ለማናገር ያደረገው ሞከራ አልተሳካም፡፡
ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ይዞት በወጣው ዘገባ ከታይላንድ ጋር በምትዋሰነው ማይናማር ውስጥ በሚገኝ ማጎሪያ ካምፕ አሁንም ከ 7 ሺ በላይ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች እንደሚገኙ ዘግቧል፡፡
እስካሁን 1 መቶ ሺ የሚገመቱ ሰዎች በደላሎች እንደተታለሉም ዘገባው አክሏል
ሊዲያ ደሳለኝ
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል !
በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ የመለያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በመለያ ምት በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል።
የመልስ ጨዋታውን አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ በመደበኛ ሰዓት ጨዋታውን 2ለ0 አሸንፏል።
የሉሲዎቹን የማሸነፊያ ግቦች አረጋሽ ካልሳ እና እፀገነት ግርማ ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በድምር ውጤት 2ለ2 መሆናቸውን ተከትሎ በተሰጠ የመለያ ምት ሉሲዎቹ አሸናፊ ሆነዋል።
ሉሲዎቹ በሁለተኛው ዙር ከታንዛኒያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር ይገናኛሉ።
ጋዲሳ መገርሳ
የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም
በዛላንበሳ እና ኢሮብ አካባቢዎች ላለው ችግር ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ።
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፀሃዩ አንባዬ ለጣቢያችን እንዳሉት ፤ ዛላንበሳን ጨምሮ በኤርትራ ሰራዊት እጅ በሆኑ የኢሮብ አካባቢዎች ያለው ችግር አሳሳቢ በመሆኑ የክልሉም ይሁን የፌድራሉ መንግስት ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በተጠቀሱት ወረዳዎች አገልግሎት መስጠት አለመቻሉንም ነግረውናል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ ፀሃዬ እንባዬ በፌደራል መንግስት እና በሕወሀት መካከል ተደርጎ በነበረው ጦርነት ምክንያት በኤርትራ ሰራዊት እጅ የገቡ አካባቢዎች ባለመለቀቃቸው የአካባቢው ተወላጆች ላይ ችግር እየደረሳባቸው እንዳሉ አንስተው ብዙዎቹም ተፈናቅለዋል ብለዋል፡፡
ሀላፊው በኢሮብ የነበረው የባንክ፣ የስልክ እና መሰል አገልግሎት በጦርነቱ ወቅት ከተቋረጠ ወዲህ ዳግም አልተመለሰም ብለዋል፡፡
ከአካባቢው የተፈናቀሉ ማህበረሰቦች በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች እና መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ እንስተው፤ ችግሩ እስካሁን ባለመቀረፉም ብዙዎቸሁ ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
በድንበር አካባቢ ያሉ ቸግሮች ተባብስው እየቀጠሉ ነው የሚሉት የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ ጸሃዬ አምባዬ የተፈናቃዮች ጉዳይም ተባብሶ ቀጥሏል ጉዳዩም ችላ ተብሏል በዚህም መንግሰት ትኩረት በመስጠት ችግሩን ሊቀርፍ ይገባል ሲሉ ከጣቢያችነ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
የዛላ አንበሳ ከተማ ከንቲባ ብርሃነ በርሄ በበኩላቸው አሁን ላይ ዛላንበሳ ከተማን ጨምሮ ምስራቃዊው ዞን ሙሉ በሙሉ በኤርትራ ጦር ቁጥጥር ስር እንደሆነ እና ነዋሪውም ብዙ በደል እና ጥቃት እየደረሰበት ነዉ ብለዋል፡፡
ለአለም አሰፋ
የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም
ከሸቀጦች የወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 84 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
ባለፉት ሰባት ወራት ከሸቀጦች የወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 84 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ(ዶ/ር) አሰታወቁ።
ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለፁት ለገቢው መገኘት ወርቅ፣ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ኤሌክትሪክና የቁም እንስሳት ኤክስፖርት ለውጤቱ መገኘት የእቅዳቸውን ከ100 በላይ ማስገኘት የቻሉ የወጪ ንግድ ምርቶች ናቸው ብለዋል።
አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው የ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ1 ነጥብ 94 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ101.2% ብልጫ አለው:: አፈፃፀሙ ይበልጥ እንድጠናከር ጥብቅ ድጋፍና ክትትል የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም
የባርሳ እና የአትሌቲ ጨዋታ 4ለ4 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ !
በስፔን ኮፓ ዴላሬ ግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 4ለ4 በሆነ አቻ ውጤት ተለይተዋል።
የባርሴሎናን ግቦች ፔድሪ ፣ ኩባርሲ ፣ ማርቲኔዝ እና ሮበርት ሌዋንዶውስኪ አስቆጥረዋል።
ለአትሌቲኮ ማድሪድ ግቦችን ጁሊያን አልቫሬዝ ፣ ግሪዝማን ፣ ሎሬንቴ እና ሶርሎት ከመረብ አሳርፈዋል።
ሁለቱ ክለቦች የመለስ ጨዋታቸውን ከአንድ ወር በኋላ በአትሌቲኮ ማድሪድ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል።
ዛሬ ምሸት 05:30 ላይ ሪያል ማድሪድ ከ ሪያል ሶሴዳድን የፋልማሉ ።
ጋዲሳ መገርሳ
የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም
የነገ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ፕሮግራሞቻችን
Читать полностью…ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ የተሻለ ጤንነት እንደታየባቸዉ ቫቲካን ዛሬ አስታወቀ።
በከፍተኛ የሳምባ ምች ሕመም ሆስፒታል በህክምና ላይ የሚገኙት፤ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ በተኙበት ሆስፒታል አዳዲስ ድንጋጌዎችን ለማጽደቅ፤ እና እጩ ቅዱሳንን ለመሰየም ከቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትላቸው ጋር መገናኘታቸዉን ቫቲካን ዛሬ አስታወቀ።
በከፍተኛ የሳምባ ምች ሕመም ሆስፒታል በህክምና ላይ የሚገኙት፤ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆኑ እየተዘገበ ነው።
ይሁን እና ዛሬ ሌሊቱን በአንጻራዊነት የተሻለ ጤንነት እንደታየባቸዉ ቫቲካን ገልጿል።
የ 88 ዓመቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ፤ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም የመተንፈስ ችግር ህመም ገጥሟቸው ሮም በሚገኘው ጌሜሊ ሆስፒታል ለህክምና ከገቡ ጊዜ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ ካቶሊክ ምዕመናን ለሃይማኖት አባታቸው ጤና ጸሎት እያደረጉ ነዉ።
የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
ኮሌራ (cholera)
የኮሌራ በሽታ ዓለም አቀፋዊ የህብረተሰብ ጤና ስጋት ስለመሆኑ የአለም ጤና ድርጅት ይገልፃል፡፡
ተመራማሪዎች እንደሚሉት በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከ 1.3 እስከ 4.0 ሚሊዮን ሰዎች በዚህ በሽታ ይያዛሉ እንዲሁም ከ 21,000 እስከ 143,000 የሚሆኑ ሰዎች ለሞት ይደርጋሉ፡፡
በአንዳንድ ሀገሮች የኮሌራ ወረርሽኝ በየጊዜው እንደሚከሰት ይነገራል፡፡
ኮሌራ በደቡብ ፣ በደቡብ ምስራቅ እስያ እና አፍሪካ ላይ ስርጭቱ ከፍተኛ መሆኑ ይነሳል፡፡
ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ለበሸታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ቢሆኑም ሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ለህመሙ የተጋለጡ መሆናቸው ይጠቀሳል ።
በጉዳዩ ላይም ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በሳንቴ ህክምና ኮሌጅ እና ህክምና ማእከል ሀኪም እና የስነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ ጋሻዬ ናቸው፡፡
ኮሌራ (cholera) ምንድን ነው?
ኮሌራ በባክቴሪያ ምክንያት በተለይም (vibrio cholera) ተብሎ በሚጠራ የባክቴሪያ አይነት የሚመጣ አጣዳፊ የተቅማጥ እና የትውከት በሽታ ነው ይላሉ፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን ኮሌራ በሰአታት ውስጥ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ በሽታ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
መንስኤው ምነድን ነው?
- የተበከለ ውሃ እና ምግብ መጠቀም
- የኮሌራ በሽታ ከያዛቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ወይም ንክኪ ካለን
- ከመፀዳጃ ቤት መልስ እጅን በሳሙና እና በንፁህ ውሃ አለመታጠብ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው ?
- ሽታ የሌለው ነገር ግን ብዛት ያለው ድንገተኛ እና አጣዳፊ ውሃማ ተቅማት መኖር
- ማቅለሽለሽ እና ትውከት
- በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ተውከት ምክንያት በሰውነታችን ውስጥ ያለው ፈሳሽ በማለቁ የከንፈር መድረቅ ፣የቆዳ መድረቅ ፣የአይን መድረቅ ፣የሽንት መጠን መቀነስ፣ፈጣን የልብ ምት፣የደም ግፊት መቀነስ ሊታይ ይችላል፡፡
- የተለመደ ባይሆንም አንዳንድ ሰዎች ላይ የሆድ ቁርጠትም ይታያል፡፡
የሚያመጣው ተፅዕኖ ምንድን ነው?
- በሰውነታችን ውስጥ ያለው ፈሳሽ በፍጥነት መቀነስ
- የተመጣጠነ ምግብ እጥረት
- ስር የሰደደ ተቅማጥ በዚሁ ሊቀጥል ይችላል
- ድንገተኛ የኩላሊት ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል
- ከፍ ካለ ደግሞ ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል ባለሙያው ያነሳሉ፡፡
ህክምናዎቹ ምንድን ናቸው?
የኮሌራ ህክምና 3 ነገሮችን አላማ ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
1 የወጣውን ፈሳሽ መተካት
2 የተፈጠረውን የኤሌክትሮ ላይት አለመመጣጠን ማስተካከል
3 ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ናቸው፡፡
እነዚህን አላማ አድርጎ ህክምናዎቹን በቤት ውስጥ እና በጤና ተቋማት መስጠት ይቻላል፡፡
በቤት ውስጥ የሚደረጉ ህክምናዎች
- ታማሚው በቂ እረፍት እንዲወስድ ማድረግ
- ኦአርኤስ መጠቀም
- እሱን ማግኘት ካልተቻለ ግን እቤታችን ውስጥ በምናገኘው ግብአት በመጠቀም ግማሽ ማንኪያ ጨው፣6 ማንኪያ ስኳር በአንድ ሊትር ንፁህ ውሀ በመበጥበጥ በተደጋጋሚ እንዲጠጣ ማድረግ
- ካፊን ያላቸው መጠጦችን እንዳይጠቀም መከልከል
- ከፍተኛ የስኳር ይዘት ያላቸውን ነገሮችም እንዳይወስድ መከልከል አስፈላጊ ነው፡፡
በጤና ተቋም የሚደረጉ ህክምናዎች
- እንዳስፈላጊነቱ መድሀኒቶችን መስጠት
- ታካሚው በአፉ መውሰድ የሚችል ከሆነ ኦአርኤስ መስጠት ካልተቻለ ግን በደም ስር የሚሰጥ ፈሳሽ ይሰጠዋል
- ፀረ ባክቴሪያል መድሃኒቶችን መስጠት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በመጨረሻም በዚህ ህመም ከመጠቃታችን በፊት ግን በሽታውን መከላከል እንደሚያስፈልግ እና ለመከላከልም የግል እና የአካባቢን ንፅህና መጠበቅ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሀ መጠቀም ፣አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ከመመገባችን በፊት በተገቢው መንገድ መታጠባቸውን እርግጠኛ መሆን ፣ጥሬ ወይም ያልበሰሉ ምግቦችን አለመጠቀም ፣መፀዳጃ ቤት ከተጠቀምን በኋላ በንፁህ ውሀ እና ሳሙና መታጠብ ፣ትክክለኛ የፍሳሽ ማስወገጃ መንገዶችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ዮናስ ተናግረዋል፡፡
ሐመረ ፍሬው
የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
የነገ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ፕሮግራሞቻችን
Читать полностью…ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሊያካሂድ ነዉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ነገ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡
ለጨረታ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 60 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፣ ጨረታው ለሁሉም ባንኮች ክፍት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡
ባንኩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ ከቅርብ ወራት ወዲህ ወርቅን ወደ ውጭ የመላክ ብቸኛ ሥልጣን ላለው ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት እጅግ አበረታች መሆኑን ገልጿል፡፡
ከባንኩ የወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማገናዘብና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ባንኮች በተቀመጠው መስፈርትና የጊዜ ማዕቀፍ መሰረት በጨረታው እንዲሳተፉ ባንኩ ጥሪ አቅርቧል::
የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም
https://ethiofm107.com/2025/02/27/የናይል-ወንዝ-ተፋሰስ-ኮሚሽን-በአንድ-አመ/
የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ደ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ስራ ይጀምራል ብለዋል።
የታይሮይድ ሆርሞን ዕጥረት( hypothyroidism)
የታይሮይድ ዕጢ ፊት ለፊት ከሚገኘው የአንገታችን ክፍል ከማንቁሪት ግርጌ የሚገኝ ለሰዉነታችን አስፈላጊ ንጥረ ቅመሞችን ( ሆርሞኖችን) የሚያመርት የአካል ክፍላችን ነዉ።
በቅርፁም ቢራቢሮ መሰል ሲሆን ክብደቱ በአማካኝ ከ 20 እሰከ 25 ግራም እንደሚመዝን ባለሙያዎች ይገልፃለ፡፡
በታይሮይድ ሆርሞን እጥረት በአለማችን ላይ ከ5 በመቶ በላይ ሰዎች እንደሚጠቁ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የስኳርና ሆርሞን ሰብ ስፔሻሊስት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መላኩ ታዬ ናቸዉ።
የታይሮይድ ሆርሞን ዕጥረት( hypothyroidism) ምንድን ነው?
የታይሮይድ ሆርሞን ዕጥረት ታይሮይድ ዕጢ በቂ ሆርሞን ማምረት ሳይችል ሲቀር የሚከሰት ችግር ነው ይላሉ፡፡
መንስኤው ምንድን ነው?
- የአዮዲን እጥረት
- የታይሮይድ ብግነት
- የታይሮይድ እጢ አፈጣጠር ችግር
- በተፈጠሩ ችግሮች እንቅርት በቀዶ ህክምና ሲወገድ በጨረር ህክምና ከተጎዳ ሊከሰት ይችላል፡፡
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
- ብርድ ብርድ ማለት፣ ቅዝቃዜን አለመቋቋም
- በቀላሉ ክብደት መጨመር፣ ብዙ የምግብ ፍላጎት አለመኖር
- የቆዳ መድረቅና አመዳምነት፣ ማሳከክ፣ የጸጉር መሳሳትና መነቃቀል
- ድባቴ፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት
- የድምጽ መጎርነን
- የሰውነት ማበጥ በተለይም በፊታችን ላይ ከአይናችን ዙርያ ማኮፍኮፍና ማበጥ
- የልብ ምት መቀነስ እና የልብ ድካም
- በሴቶች ላይ የወር አበባ መዛባት
- የሆድ ድርቀት ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች ናቸው፡፡
ህክምናዎቹ ምንድን ናቸው?
የታይሮይድ ሆርሞን ዕጥረት የሚታከመው ያነሰውን ሆርሞን በሰውሰራሽ የታይሮይድ ሆርሞን መድሃኒቶች በመተካት ነው። ከአንዳንድ ጊዜያዊ የሆርሞን መዛባት ምክንያቶች በስተቀር የዕድሜ ልክ ህክምና ይፈልጋል። የሆርሞን ህክምናው በትክክል ከተወሰደ ጤናማ ሕይወት መቀጠል እንደሚቻል ባለሙያ ይናገራሉ ፡፡
በመጨረሻም ማንኛውም ሰው ግልጽ ያልሆኑ የህመም ምልክቶች ካለው፣ ያልተለመደ የድካም ስሜት ከበዛ፣ ብዙ ሳንበላ ክብደት ከጨመረ ወይም የማስታወስ ችግር ካጋጠመ የታይሮይድ ሆርሞን ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ዶ/ር መላኩ ተናግረዋል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
ሃማስ የአራት ታጋቾችን አስከሬን ካስረከበ በኋላ እስራኤል የፍልስጤም እስረኞችን ፈታች።
ሃማስ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስረኞች ምትክ የአራት እስራኤላውያንን የጋዛ ታጋቾች አስከሬን አስረክቧል፡፡
እ.ኤ.አ. በጥቅምት 7 ቀን 2023 አድርሱት በነበረው ድንገታዊ ጥቃት በሃማስ የተወሰዱት የአራቱን ዜጎቿን አስክሬን ለማረጋገጥ ምርመራ እንደምታደርግ እስራኤል አሳውቃለች፡፡
ሃማስ የአራቱን ታጋቾች አስከሬኖች ያስረከበው ህዝብ ሳይሰበሰብና የመድረክ ትዕይንት ሳያዘጋጅ ሲሆን እስራኤል መሰል ዝግጅቶች ከተደረጉ እስረኞችን አለቅም በሚል ማስጠንቀቋ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነም ተዘግቧል፡፡
እስራኤል የፍልስጤሙ ቡድን ታጋቾችን ሲያስረክብ "የዜጎቼን ክብር ዝቅ የሚያደርግ" ዝግጅት ማካሄድ የለበትም በሚል ባለፈው ሳምንት ልትለቃቸው የነበሩ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ሳትፈታ መቆየቷ ይታወሳል።
በግብጽ አደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነትም ዛሬ ላይ እስራኤል ከ600 በላይ የፍልስጤም እስረኞችን መልቀቅ የጀመረች ሲሆን አብዛኛዎቹም ወደ ዌስት ባንክ እና ጋዛ ሲመለሱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ከአደባባይ በመውጣት በደስታ እንደተቀበሏቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለሰባት ሳምንታት በዘለቀው የመጀመሪያ ምዕራፍ ስምምነት ሃማስ 34 በህይወት ያሉ እና 10 የታጋቾች አስከሬን አስረክቧል፤ እስራኤል ደግሞ ዛሬ የምትለቃቸውን ጨምሮ 1700 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።
ቀሪዎቹን 59 ታጋቾች ለማስለቀቅ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መራዘም ይኖርበታል።
እስራኤልና ሃማስ በጥር ወር መጨረሻ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ የፊታችን ቅዳሜ ይጠናቀቃል።
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
በ27ተኛ ሳምንት የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐግብሮች አርሰናል ነጥብ ሲጥል ሊቨርፑል፣ማንችስተር ሲቲ እና ማንችስተር ዩናይትድ ማሸነፍ ችሏል ።
ሊቨርፑል ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር ያደረገውን የሊግ ጨዋታ ሊቨርፑል 2ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
የሊቨርፑልን የማሸነፊያ ግቦች ማክ አሊስተር እና ዶምኒክ ስቦዝላይ ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል።
የሊጉ መሪ ሊቨርፑል ማሸነፉን ተከትሎ ከተከታዩ አርሰናል ያላዉን የነጥብ ልዩነት ወደ አስራ ሶስት ማስፋት ችለዋል።
አርሰናል ከኖቲንግሀም ፎረስት ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቀዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ ከኢፕስዊች ታውን ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 3ለ2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
የማንችስተር ዩናይትድን ግቦች ሀሪ ማጓየር ፣ ዴሊት እና ሞርሲ ከመረብ ማሳረፍ ሲችሉ ለኢፕስዊች ሁለቱንም ግቦች ጃደን አስቆጥሯል።
ማንችስተር ሲቲ በበኩሉ ከቶተንሀም ጋር ያደረገውን ጨዋታ በኤርሊንግ ሀላንድ ግብ 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል።
ኤርሊንግ ሀላንድ በውድድር ዘመኑ 20ኛ የሊግ ግቡን አስቆጥሯል።
በሌላ ጨዋታ ብሬንትፎርድ ከኤቨርተን ጋር 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
የሊግ ደረጃቸው
1 ሊቨርፑል:- 67 ነጥብ
2 አርሰናል :- 54 ነጥብ
3 ኖቲንግሀም ፎረስት :- 48 ነጥብ
4 ማንችስተር ሲቲ :- 47 ነጥብ
5 ቼልሲ:- 46 ነጥብ
6 ኒውካስል ዩናይትድ :- 44 ነጥብ
13 ቶተንሀም :- 33 ነጥብ
14 ማንችስተር ዩናይትድ :- 33 ነጥብ
ጋዲሳ መገርሳ
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
የነገ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ፕሮግራሞቻችን
Читать полностью…ከመተሃራ እስከ ባቡር ትራክሽን ጣቢያ አስደንጋጭ ዝርፊያ እንደተፈጸመበት ተነገረ
ባለፉት አስር ቀናት በቡድን በተደራጀ ሁኔታ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ የኮንዳክተር ሽቦ ገመድ እና 25 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የኦ.ፒ.ጂ ደብሊው ፋይበር መስመር ለስርቆት መዳረጋቸውን የአዋሽ - ወልዲያ - ሃራ ገበያ የባቡር የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ቢሮ አስታወቀ።
በተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንደተናገሩት በፕሮጀክቱ ላይ የተፈፀመው የስርቆት ወንጀል እጅግ አስደንጋጭ ነው።
በቢሮው የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለወይን ብርሃነአሰፋ እንደተናገሩት ባለፉት አስር ቀናት ከመተሃራ እስከ ባቡር ትራክሽን ጣቢያ አንድ ድረስ በቡድን በተደራጀ ሁኔታ 78 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የኮንዳክተር ሽቦ እና 25 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ዝርፊያ ተፈጽሟል።
በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በዱዱብ እና ዶሆ ቀበሌዎች ሁለት ጊዜ እንዲሁም በዱለሳ ወረዳ በቡሩቱሊ እና ኢስኪለሊ ቀበሌዎች አንድ ጊዜ በተፈፀመ የስርቆት ወንጀል ሳቢያ ከ758 ሺህ ዶላር በላይ እና በብር ከ6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን ተናግረዋል።
የስርቆት ወንጀሉ የተፈፀመው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ወደ ሥራ እስኪገባ ድረስ በ33 እና 15 ኪሎ ቮልት በጊዜያዊነት ኃይል ይዞ እንዲቆይ ለማድረግ ከሥራ ተቋራጩ ጋር ምክክሮች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት መሆኑ እንዳሳዘናቸውም ገልፀዋል።
እንደ ሳይት ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ዝርፊያ ተፈፅሞባቸው በአይሱዙ መኪና ተጭነው ሲጓዝ የነበረ የኮንዳክተር ሽቦ በአዳማ ከተማ ላይ እንዲሁም በዱለሳ ወረዳ መቁረጫ ሴጌቶ ይዘው የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ክስ ለመመስረት ማስረጃ እየተደራጀ ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም
ቼልሲ ከሶስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል !
የለንደኑ ክለብ ቼልሲ ከሳውዝሀምፕተን ጋር ያደረጉትን የፕርሚየር ሊግ መርሐ ግብር 4ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
የቼልሲን የማሸነፊያ ግቦች ክርስቶፈር ንኩንኩ ፣ ፔድሮ ኔቶ ፣ ሌቪ ኮል ዊል እና ኩኩሬላ ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል።
ሳውዛምፕተን በውድድር ዘመኑ ሀያ ሁለተኛ ሽንፈቻቸውኝ አስተናግደዋል።
በሌሎች ጨዋታዎች
- ክሪስታል ፓላስ አስቶን ቪላን 4ለ1
- ፉልሀም ዎልቭስን 2ለ1
- ብራይተን በርንማዝን 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል፡፡
ሊጉ ዛሬም ሲቀጥል-፡
04:30 | ብሬንትፎርድ ከ ኤቨርተን
04:30 | ማንችስተር ዩናይትድ ከ ኢፕስዊች
04:30 | አርሰናል ከ ኖቲንግሃም
04:30 | ቶተንሀም ከ ማንችስተር ሲቲ
05:15 | ሊቨርፑል ከ ኒውካስትል
ጋዲሳ መገርሳ
የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም
የብሔራዊ ባንክ የ60 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ ተጠናቀቀ
በጨረታውም አንድ የአሜሪካ ዶላር በአማካይ 135 ብር ከ61 ሳንቲም ዋጋ መሸጡንም ባንኩ አስታውቋል ፡፡
ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ባካሄደው ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ውጤት መሰረት፣ የአንድ የአሜሪካ ዶላር አማካይ የምንዛሪ ዋጋ 135 ነጥብ 6185 ብር መሆኑን ይፋ አድርጓል።
በዚህ ጨረታ 27 ባንኮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሳትፎ መኖሩን ገልጿል። ባንኩ አክሎም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና ከዋጋና ከውጭ ምንዛሪ መረጋጋት ጋር በሚስማማ መልኩ ተጨማሪ ጨረታዎችን እንደሚያካሂድ አስታውቋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ትግበራ ከገባ ካለፈው ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ የአሁን የውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጨረታ ሲወጣ ለ2ኛ ጊዜ መሆኑ ይታወቃል ።
የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
ኢዜማ የመንግስት አካላት በሚል በጠራቸው የፀጥታ ኃይሎች በአዲስ አበባ ውስጥ ወጣቶች እየታፈኑ እና የት እንዳሉ ማወቅ አሰቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ቀናት በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ወጣቶች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየታፈኑ የት እንደገቡ ሳይታወቅ መሰወራቸውን ከቤተሰቦቻቸው እና ከተለያዩ አካላት ለመገንዘብ ችያለሁ ብሏል ኢዜማ፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዛሬ በሕግ መጠየቅ ያለበት የትኛውም ዜጋ በሕግ ሊጠየቅ የሚገባው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው በሚል ዛሬ ሰፊ መግለጫ አስነብቧል፡፡
ባለፉት ጥቂት ቀናት በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ወጣቶች ኢዜማ የመንግስት አካላት የፀጥታ ኃይሎች እየታፈኑ የት እንደገቡ ሳይታወቅ መሰወራቸውን ከቤተሰቦቻቸው እና ከተለያዩ አካላት ለመገንዘብ መቻሉን በመግለጫው አትቷል፡፡
ይኽን የመንግሥት ተግባር ይበልጥ አስከፊ የሚያደርገው እነዚህ ታፍነው የተወሰዱ ወጣቶች የት እንደሚገኙ አለመታወቅና ቤተሰቦቻቸውም በመንግሥት አካል የተያዘ ግለሰብ ሊገኙባቸው ይችላሉ የሚሏቸውን ቦታዎች ቢያስሱም ለማግኘት አለመቻላቸው ነው ሲል ገልጻል።
ይህ ብቻ አይደለም አንዳንዶቹ ከተወሰኑ ቀናት መሰወር በኋላ በድንገት የት እንደነበሩ እንኳ መናገር በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ወደቤታቸው መመለሳቸው ማወቅ ችያለሁ ብሏል፡፡
አሁንም በዚህ አይነት አፈና ውስጥ ያሉ ወጣቶች እንዳሉ ፓርቲያችን አረጋግጧል ካለ በኃላ ቤተሰቦቻቸውም በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸል፡፡
የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
‹‹ስለህዳሴ ግድብ ለማዉራት ወደሌሎች ሀገራት አንሄድም›› አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)
ታላቁ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 98.13 በመቶ መድረሱ ተናግረዋል፡፡ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት መሆኑን የጠቀሱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ :: ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለማዉራት ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ እንጂ እኛ ወደሌላ አንሄድም ሲሉ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናግረዋል፡፡
ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የመደራደር አቅምን ፈጥሯል ነዉ ያሉት ሚኒስትሩ ህዳሴ ግድብ ሲገነባ የታችኛዉን ተፋሰስ ሃገራት በማይጎዳ ይልቁንም በሚጠቅም መንገድ ነዉ ታስቦ የተሰራዉ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ የኢትዮጵያን የመልማት መብት የሚያረጋግጥና የቀጣናውን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑንም አንስተዋል።
ለተስተካከለ የውሃ አቅርቦት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅንና ድርቅን ለመከላከል ይረዳልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአለም ሃገራት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እርዳታን ባቋረጡበት ወቅት እና የተለያዩ ሀገራት ሴራዎች በሸረቡባት በዚህ ጊዜ የህዳሴ ግድብን እዉን ማድረጓ ትልቅ አቅምን ፈጥሮላታል ሲሉ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢታፋ ተናግረዋል፡፡
ልኡል ወልዴ
የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ውሳኔ አስተላለፈ
የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር የፋይናንስ አጣሪ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ የፋይናንስ ደንብ በጣሱ ክለቦች እና ተጨዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል።
- ኮሚቴው በመግለጫው 4 ክለቦች እና 15 ተጫዋቾች ህገ ደንቡን ጥሰዋል ብሏል።
- መቻል ስፖርት ክለብ 17 ተጫዋቾች ቅድመ ክፍያ(በሶስተኛ ወገን) በመክፈሉ
- ቅድመ ክፍያ በሰጣቸው 7 ተጫዋቾች በአጠቃላይ ብር 21,000,000 እንዲቀጣ።
- ሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ለ6 ተጫዋቾች ቅድመ ክፍያ(በሶስተኛ ወገን) በመክፈሉ
- ክለቡ ቅድመ ክፍያ በሰጣቸው 6 ተጫዋቾች በአጠቃላይ ብር 18,000,000 እንዲቀጣ።
- መቐለ 70 እንደርታ ስፖርት ክለብ እና ሀዋሳ ስፖርት ክለብ ለአንድ ተጫዋች ቅድመ ክፍያ(በሶስተኛ ወገን) በመክፈሉ በአንቀጽ 9 መሰረት ብር 3,000,000 እንዲቀጣ።
- ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ክለቡ በ2017 የውድድር ዘመን የተጫዋቾች ዝውውር እንዳያደርግ እንዲታገድ ተወስኗል።
ሁሉም የህግ ጥሰቱን የፈፀሙ ተጨዋቾች - ለፈፀሙት ጥፋት 200,000 ብር እንዲከፍሉ
- ቅድመ ክፍያውን ተመላሽ እንዲያደርጉ ተመላሽ ያደረጉበትን ማስረጃ እስኪያቀርቡ ድረስ ከውድድር ታግደው እንዲቆዩ ወስኗል።
ጋዲስ መገርሳ
የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
በሕገ-ወጥ ተግባር የተሰማሩ የነዳጅ ኩባንያዎችና በሥራቸው የሚገኙ ማደያዎች በፍጥነት ወደ ሕጋዊነት እንዲገቡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከነዳጅ ኩባንያ ባለቤቶችና ሃላፊዎች ጋር በነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በነዳጅ ኩባንያዎች፣ በነዳጅ ማደያዎችና እና በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አደረጃጀቶች በኩል ያሉ ውስንነቶች ዙሪያ መክረዋል፡፡
መንግስት ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ብዙ ቢሊየን መዋዕለ ንዋይ እየደጎመ ነዳጅን አቅርቧል ያሉት ሚኒስትሩ÷ በዚህ መልኩ የገባን ነዳጅ በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ተዋንያን እንዳሻቸው ሊያደርጉት አይገባም ብለዋል፡፡
በውይይቱ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ የነዳጅ ኩባንያዎች እና በሥራቸው የሚገኙ ማደያዎች በፍጥነት ወደ ሕጋዊነት እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡
ነዳጅ በሕገ-ወጥ መንገድ በችርቻሮ የሚሰራጭበትን ሁኔታ ለማስቆም የተጀመሩ ርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረትን በመፍጠር ያልተገባ ትርፍ ለማጋበስ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደማይታገስም አስታውቀው፤ ከዚህ በኋላ ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል ጨክነን ተገቢውን ርምጃ እንወስዳለን ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም