5 የአውሮፕላን ማረፊያዎችን እየገነባሁ ነው- የኢትዮጵያ አየር መንገድ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አምስት ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየሰራ ነው።
የሚያበራቸውን አውሮፕላኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ አየር መንገዱ 136 ዓለም አቀፍ እንዲሁም 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት የያዘውን ዕቅድ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት አምስት የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤርፖርቶቹ የሚገነቡት ሚዛን ቴፒ አማን፣ ነጌሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ጎሬ መቱና ደብረ ማርቆስ መሆናቸውን ገልጸው፤ አራቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።
ይህም በሀገር ውስጥ ያሉ ደንበኞች ፍላጎትን ተከትሎ የሚተገበር ሲሆን፤ በቀጣይም ሌሎች መዳረሻዎች ጥናት ላይ በተመሠረተ መልኩ ግንባታ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል ጉዳት የደረሰባቸው የአክሱምና የቀብሪደሃር ኤርፖርቶች እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በቀጣይም የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።
የህዳሴ ግድብ 5 ተርባይኖች በመጪዎቹ ሳምንታት ሀይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተባለ
ግንባታው ባይጠናቀቅም በ 2 ተርባይኖች ሀይል ማመንጨት ጀምሯል የተባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በመጪዎቹ ሳምንታት 5 ሀይል አመንጪ ተርባይኖች ስራ እንደሚጀምሩ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት መግለፁን ሸገር ኤፍ ኤም ዘግቧል።
የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ 13 ተርባይኖች ሀይል ማመንጨት ሲጀምሩ አጠቃላይ የግድቡ ስራ የሚጠናቀቅ መሆኑን የገለፁ ሲሆን 5 ሀይል አመንጪ ተርባይኖች በቀጣይ ሳምንታት ስራ እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ለጅቡቲ፣ ለሱዳን እና ለኬንያ የኤሌክትሪክ ሀይል እየተሸጠ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር አረጋዊ፤ ለታንዛኒያ እና ለደቡብ አፍሪካ ለመሸጥ ታቅዶ ንግግር ተጀምሯል ብልዋል፡፡ ለተገባደደው የግድቡ ስራ አሁን የሚቀሩት በአብዛኛውም ከውጭ የሚገቡ የመካኒካል እና ኤሌክትሪካል ግብአቶች መሆናቸውና አጠቃላይ ግንባታውም፤ በ1 ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መገመቱም ነው የተገለፀው።
ኢትዮጵያ፦ የእለተ ማክሰኞ ኢትዮትዩብ አንኳር አጫጭር ዜናዎች - መጋቢት 10 ፣ 2016 | #Ethiopia: EthioTube Ankuar : አንኳር - Ethiopian Daily News Digest - March 19, 2024
👉 ሸዋሮቢት ፋኖና መከላከያ መካከል ያለው ውጥረት ቀጥሏል
👉የቲቪ ጣቢያዎች ለሚለቁት ሙዚቃ ክፍያ ሊፈጽሙ ነው
👉 የመሬት ዞታና ካሳን በተመለከተ ዛሬ የቀረበው ረቂቅ
ሌሎችንም መረጃዎች ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/1pZTm9buZYw
የአውሮጳ ህብረት እና ግብፅ ስደትን ለመግታት የ8 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ
የአውሮጳ ህብረት እና ግብፅ በንግድ እና በፀጥታ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ እንዲሁም ወደ አውሮጳ የሚደረገውን የስደተኞች ፍሰት ለመግታት ያለመ የ7.4 ቢሊዮን ዩሮ ወይም የ8 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርመዋል።ስምምነቱ የአውሮፓ ህብረት ከግብፅ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ ያደርገዋል።
የግብፅን የኢኮኖሚ ውድቀት ለመደገፍ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት እርዳታ፣ብድር እና ሌሎች ድጋፎችን ያገኛከል ።የሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ግብፃውያን ወደ አውሮፓ በተለይም በሊቢያ በኩል ለመሻገር ይሞክራሉ፡፡ባለሥልጣናቱ ከግብፅ ሰሜናዊ የባህር ዳርቻ የሚወስደውን መንገድ ዘግተዋል፡፡
ግብጽ ወደ አውሮፓ የሚደረገውን መደበኛ ያልሆነ ስደት ለመግታት እንደምትሰራም አስታዉቃለች፡፡የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ "ይህ በልማት ላይ ያተኮሩ መፍትሄዎችን በመጠቀም የችግሩን መንስኤ መፍታት እና መደበኛ የስደት መስመሮችን ማሻሻልን ያጠቃልላል" ብለዋል ።
የአውሮፓ ህብረት ቀደም ባሉት ጊዜያት ቱኒዚያ፣ ሊቢያ እና ሞሪታንያን ጨምሮ ወደ አውሮፓ ለሚደረጉ መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰት ታዋቂ መንገዶች ከሚሆኑት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ተመሳሳይ ስምምነቶችን ተፈራርሟል።
ምክር ቤቱ 18ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ያካሂዳል
በስብሰባውም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ /ማሻሻያ/ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ማርዋን ኢሳ የተባለው የሐማስ ከፍተኛ የጦር መሪ መገደሉን አሜሪካ አስታወቀች
የሐማስ ከፍተኛ የጦር መሪ ማርዋን ኢሳ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን የዋይት ሃውስ ባለሥልጣን ጃክ ሱሊቫን ተናገሩ።
ምክትል የጦር አዛዡ ኢሳ በእስራኤልና በሐማስ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተገደለ ከፍተኛው የጦር መሪ ነው።
ጋዛን የተቆጣጠረው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን የጦር መሪው ሞቷል ስለመባሉ በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።
የእስራኤል የመገናኛ ብዙኃን ምንጮች ኢሳ ከአንድ ሳምንት በፊት እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኘው ኑሴራት የስደተኞች ካምፕ የሚገኝ ዋሻን ኢላማ አድርጋ በፈፀመችው የአየር ጥቃት መገደሉን ዘግበዋል።
የሐማስ የጦር ክንፍ የሆነው ኢዘዲን አል ቃሳም ብርጌድ ምክትል አዛዥ በእስራኤል በጥብቅ ከሚፈለጉ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር።
የአውሮፓ ሕብረት 1 ሺህ 200 ሰዎችን ከገደለው እንዲሁም ጦርነት ከቀሰቀሰው ከጥቅምት ሰባቱ ጥቃት ጋር በተያያዘ የሐማሱን መሪ በሽብርተኛ መዝገብ ውስጥ አካቶታል።
የጦር መሪው በመጀመሪያው የፍልስጤም ተቃውሞ ወቅት ለአምስት ዓመታት በእስራኤል ታስሮ ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ 1997ም በፍልስጤም ባለሥልጣን በቁጥጥር ሥር ውሎ ሁለተኛው የፍልስጤም ተቃውሞ እስከጀመረበት 2000 ድረስ በእስር አሳልፏል።
ጥቅምት ሰባት ላይ ሐማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በመግባት ጥቃት ፈፅሞ እስራኤል የአፀፋ ምላሽ መስጠት ከጀመረች ወዲህ በርካታ የሐማስ ከፍተኛ መሪዎች ተገድለዋል።
ከእነዚህ መካከል በቤሩት ደቡባዊ ከተማ ዳህየህ በደረሰ ፍንዳታ የሞተው የሐማስ የፖለቲካ መሪ ሳሌህ ኣል አሮሪ ይገኝበታል።
የዋይት ሃውስ የጸጥታ አማካሪ ሱሊቫን እንዳሉት ሌሎች የሐማስ መሪዎችም በጋዛ ጥልቅ በሆነ የኔትዎርክ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው እንደሚገኙ ይታመናል።
አማካሪው፣ አሜሪካ እስራኤል ከፍተኛ የሐማስ መሪዎችን ለማደን ለምታደርገው ዘመቻ ድጋፍ እንደምታደርግም ቃል ገብተዋል።
የዓባይ ግድብ የኤሌክትሪክ ማመንጫው ግንባታ በሰባት ወራት ይጠናቀቃል ተባለ
የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታው በሰባት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅና በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ሙሉ ሥራ በቀጣይ ዓመት እንደሚጠናቀቅ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
የግድቡ ግንባታ የሲቪል ሥራው 99 በመቶ ተጠናቅቋል የተባለ ሲሆን ዋናው የግድቡ ክፍል 107 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት እንደሚይዝና ከዚህ ውስጥ አንድ በመቶው ሥራ ብቻ እንደሚቀር ተጠቁሟል። የግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል በተለይም የተርባይንና ጄኔሬተር ተከላ ሥራው 78 በመቶ መጠናቀቁም ተገልጿል።
የግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ እንደተጀመረ የሚታወስ ሲሆን በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ 95 በመቶ መድረሱም ነው የተገለፀው።
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ዩክሬን እና ሉሎች ምእራባውያን ሀገራት አስተያየት ሰጥተዋል።
የሩሲያ ማእከላዊ የምርጫ ኮሚሽን ሰብሳቢ እንዳስታወቁት፤ እስካሁን በተደረገ የድምጽ ቆጠራ ቭላድሚር ፑቲን 88 በመቶ ደምጽ በመግኘት በሰፊ ልዩነት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል።
በዚህም ፑቲንእስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ማለትም ለቀጣይ 6 ዓመታት በስልጣን ላይ የሚቆዩበትን እድል በድጋሚ አግኝተዋል ነው የተባለው።
ይህንን ተከትሎም ዩክሬን፣ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ፖላድ እና ሌሎችም ሀገራት ውጤቱን ተችተው አስተያየት ከሰጡ ሀገራት መካከል ናቸው።
*አሜሪካ*
የአሜሪካ ዋይት ኃውስ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ ምርጫው ነጻ እና ግልጽ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ፑቲን የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን በማሰር እና ሌሎቹንም ከምርጫው በማግለል ነው ያሸነፈው ብለዋል።
*ዩክሬን*
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በሰጡት መግለጫ፤ “የሩሲያው አምባገነን መሪ ቭላድሚር ፑቲን ሌላ የማስመሰል ምርጫ አድርጓል” ብለዋል። “ፑቲን ያደረገው ነገር የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ያደረገው እንደሆነ ዓለም ሁሉ ያውቀዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
“በዚህ የማስመሰል ምርጫ ምንም ህጋዊ ነገር የለም፤ ሊኖረውም አይችልም” ያሉት ዘለንስኪ፤ “ፑቲን መቅረብ ያለበት ዘ ሄግ በሚገኘው ችሎት ነው፤ ይህንንም ልናረጋግጥ ይገባል” ብለዋል።
*ጀርመን*
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤከስ ገጽ ባወጣው መግለጫ፤ “ሩሲያ ያካሄደችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነጻ ገለልተኛም አይደለም፤ ውጤቱም ማንንም አላስገረመም” ብሏል።
“የፑቲን አገዛዝ አምባገነናዊ ነው” ያለችው ጀርመን፤ አገዛዙ በሳንሱር፣ በጭቆና እና በአመጽ ላይ የተመሰረተ ነው” ስትልም ገልጻች።
ሩሲያ በያዘቻቸው ዩክሬን ግዛቶች ያደረገችው ምርጫም ባዶ እና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ብሏል የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው።
*ብሪታኒያ*
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በሩሲያ ምርጫ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “በሩሲያ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተጠናቋል፤ በሩሲያ በተያዙ ዩክሬን አካባቢ ያሉ ሰዎችም ያለ ምንም አማራጭ ለመምረጥ ተገደዋል፤ ይህ ምኑም ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫን አይመስልም” ብለዋል።
ምእራባውያን እና ዩክሬን ምርጫው ነጻ እና ፍትሃዊ አይደልም ብለው ቢያጣጥሉትም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ሩሲያ ያካሄደችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከየትኛውም የምእራባውያን ሀገራት የተሸለ እና በጣም ግልጸኝነት የታየበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ከተወለደ በግምት የሶስት ቀን እድሜ ያለዉ ልጅ ወንዝ ዉስጥ ተጥሎ ህይወቱ አልፎ ተገኘ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ሁልባራግ ወረዳ በቶዴ ጠመዳ ቀበሌ ልዩ ቦታዉ አባይነህ አበጋዝ ተብሎ በሚጠራው መንደር በራመቴ ወራጅ ወንዝ ላይ ተጥሎ ህይወቱ ያለፈ ህፃን መገኘቱን የዞኑ ፖሊስ አስታዉቋል።
የስልጤ ዞን ፖሊስ መምሪያ ህዝብ ግንኙነትና ሚድያ ጉዳዮች ድቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ከድር ኤርጎሻ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በግምት የሶስት ቀን ዕድሜ የለው የሚሆን ህፃን ልጅ ውሀ ውስጥ ተጥሎ ከብት የሚጠብቁ ህፃናት ውሀው ውስጥ መገኘቱን ተናግረዋል።
ህጻናቱ ክስተቱን በአፋጣኝ ለቤተሰባቸው በመጠቆማቸው እና ይህንንም የሰሙት የማህበረሰብ ክፍሎች ለወረዳው ፖሊስ መረጀ በመስጠት ፖሊስ በቦታዉ መድረሱን አስረድተዋል።
በቦታዉ የደረሰዉ የወረዳው ፖሊስ የህጻኑን አስክሬን ከወንዝ ውስጥ በማውጣት ወደ ወራቤ ሆስፒታል ወስዶ አስክሬኑን ካስመረመ በኋላ የወረዳው ፖሊስ ከከተማዉ ማዘጋጃ ቤት ጋር በመተባበር አስክሬኑ በክብር መቅበሩን ኮማንደሩ አስረድተዋል።
ፖሊስ የህጻኑን ወላጅ እናት ለማወቅ ስራዎቹ ከባድ እንደሆኑበት ገልጾ ወላጅ እናቱን ለመለየት ተጠርጣሪዎችን የመለት ስራ በመስራት ላይ መሆኑን የስልጤ ዞን ፖሊስ መምሪያ ህዝብ ግንኙነትና ሚድያ ጉዳዮች ድቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ከድር ኤርጎሻ ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
Facebook.com/EthioTube
Twitter.com/EthioTube
Youtube.com/EthioTube
Instagram.com/EthioTube
/channel/ethiotube
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር አመሰገኑ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮንን አመሰገኑ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "በኢትዮጵያ የአለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን በኢትዮጵያ የቆይታ ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ ምስጋናችንን እናቀርባለን። ላለፉት ጥቂት አመታት ላደረጉት ያላሰለሰ ድጋፍዎ እናመሰግናለን።" ሲሉም አመስግነዋል።
በአሶሳ ዞን በግለሰብ ማሳ ውስጥ እየለማ የነበረ የካናቢስ አደንዛዥ ዕፅ ተክል በቁጥጥር ስር ዋለ
በአሶሳ ዞን በመንጌ ወረዳ ሸንዲ ቀበሌ
በግለሰብ እርሻ ማሳ ውስጥ እየለማ የነበረ በርካታ የካናቢስ አደንዛዥ ዕፅ ተክል በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን የመንጌ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታውቋል ።
የአደንዛዥ ዕፁ ተክሉ በወረዳው ሸንዲ ቀበሌ አትያሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ግለሰብ እርሻ ማሳ በመልማት ላይ እያለ የተያዘ መሆኑን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር አሳድቅ አብዱልፈታህ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።
ተጠርጣሪው ግለሰብ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ እጅ ከፈንጅ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በህግ አግባብ እየታየ እንደሚገኝ አክለዋል ።
ይህን መሰሉ ድርጊት የመጀመሪያ አይደለም ያሉት ረዳት ኢንስፔክተር አሳድቅ አካባቢው የሱዳን ድንበር ስለሆነ አደንዛዥ ዕፅ ለማሻገር ሲሞከር በተደጋጋሚ በቁጥጥር ሲር ማዋል መቻሉን ጠቁመዋል ።
ህብረተሰቡ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ሂደት ጥቆማ በመስጠት መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል ።
ኢትዮጵያ ለአገር ውስጥ መጓጓዣነት የሚያገለግሉ ሁለት ጀልባዎችን ገዛች
የኢትዮጵያ መንግስት ለአገር ውስጥ የውሃ መጓጓዣ የሚሆኑ ሁለት ጀልባዎችን መግዛቱን የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አስታወቀ።
ከአንድ ዓመት በፊት ድርጅቱ 'ጣናነሽ 2' እና 'መደመር' የተሰኙ ሁለት ጀልባዎች ግዢ እየተፈጸመ እንደነበር ተገልጾ ነበር። የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሁለት ጀባዎች መጫናቸውን ቢገልጽም የ'ጣናነሽ 2' ስም ተጠቅሶ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
ከሦስት ሳምንታት በኋላ ጅቡቲ ወደብ እንደሚደርሱ ከተገለጹት ሁለት መርከቦች አንዱ 'ጣናነሽ 2' 38 ሜትር ርዝመት ሲኖረው በአንድ ጊዜ 188 ሰዎችን የመጫን አቅም እንዳለው የተገለጸ ሲሆን በ'አሶሳ መርከብ' ተጭና ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ መጀመሯን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በ1942 ዓ.ም ጣሊያናዊያንና ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ተሰባስበው ጣና ላይ መሰረታቸውን አድርገው የፈጠሩት 'ናቪጋ ጣና' የባህር ትራንስፖርት ድርጅት፤ በሕዳር ወር 2015 ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ከጣና ሐይቅ በመጀመር በአገር ውስጥ የውሃ ጉዞ አገልግሎት ለመስጠት ተዋህደዋል።
ወታረዳዊ ሚስጦሮችን ለቻይና የሸጠ አሜሪካ ጦር አባል በቁጥጥር
ስር ዋለ
ሳጅን ኮብሪን ጥብቅ ወታራዊ ሚስጥሮች በ42 ሺህ ዶላር ለቻይና መሸጡ ተነግሯል
የአሜሪካ ጦር የደህንት ጉዳዮች ተንታኝ የሆነው ሳጅን ኮብሪን ሽልዝ ሚስጥራዊ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎች ለቻይና በመሸጥ በቁጥጥር መዋሉ ተገለጸ።
ሳጅን ኮብሪን ሽልዝ የኤፍ.ቢ.አይ እና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በጋራ ያደረጉትን ምርመራ ተከትሎ ትናንት ሐሙስ በኬንታኪ ፎርት ካምቤል በቁጥጥር ስር መዋሉም ተነግሯል።
በቀረበው ክስ መሰረትም ሳጅን ኮብሪን ለቻይና አሳልፎ በሰጣችው እጅግ ሚስጥራዊ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎች ምትክ 42 ሺህ ዶላር እንደተከፈለው ተመላቷል።
ተከሳሹ መረጃዎች አሳልፎ የመስጠት ወንጅሉን ከሰኔ ወር 2022 ጀምሮ እስከ ታሰረበት ድረስ ሲያከናውን መቆየቱንም ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ሳጅን ሽልዝ የሀገር መከላከያ ቴክኒካዊ መረጃዎችን ያለፍቃድ ወደ ውጭ በመላክ፣ እንዲሁም በመንግስት ላይ በማሴርና ጉቦ በመቀበል ወንጀሎች እንደተከሰሰም ተነግሯል።
ሳጅን ስቸልዝ ለቻይና አሳልፎ ሸጧል ከተባሉት ሚስጥራዊ መረጃዎች መካከልም፤ ስለ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ምርት እቅድ፣ በዩክሬን ጦርት ላይ የአሜሪካ የወደፊት እቅድ፣ ቻይና ታይዋንን ከወረረች አሜሪካ ስለምትወስደው እርምጃ እና ሌሎችንም ያከተተ ነው ተብሏል።
አፍ.ቢ.አይ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት፤ “የቀረበው ክስ ግለሰቡ ሀገሩን ለመጠበቅና ለመከላከል
የገባው ቃል ኪዳን ላይ ከባድ ክህደት መፈጸሙን ያመለክታል” ብሏል።
የሀገር መከላያ ሚስጠር መጠበቅ ሲገባው ከውጭ ኃሎች ጋር በማሴር እና ሚስጥራዊ መረጃዎች በመሸጥ የሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንት አደጋ ላይ መጣሉንም ኤፍ.ቢ.አይ አስታውቋል።
አል አይን
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፒያሳ ለሚነሱ የግል አልሚዎች “ካሳ እና ምትክ መሬት” እንደሚሰጥ አስታወቀ!
በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ከተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ጎን በሚገኘው ቦታ ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች፤ ከስፍራው እንደሚነሱ የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አበቤ ማረጋገጫ ሰጡ። ለእነዚህ የልማት ተነሺዎች የከተማው አስተዳደር “የጋራ መኖሪያ ቤት” አሊያም “አዲስ የሚገነባ የቀበሌ ቤት” እንደ የምርጫቸው እንደሚያቀርብ፤ በአካባቢው በተዘጋጀው ፕላን መሰረት ግንባታ ለማከናወን የገንዘብ አቅም ለሌላቸው የግል አልሚዎች ደግሞ “ካሳ እና ምትክ መሬት” እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
አዳነች ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኙ “የመንገድ ኮሪደር ልማት” ስራዎችን በተመለከተ በሰጡት ገለጻ ነው። በመንግስት እና ለመንግስት ቅርበት ባላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በትላንትናው ዕለት በተላለፈው በዚህ ገለጻ፤ የኮሪደር ልማቱን የተመለከተ ጥናት ሲከናወን የቆየው ከግንቦት 2015 ጀምሮ መሆኑ ተጠቅሷል።
ይህ የመንገድ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከጸደቀ ማግስት ጀምሮ “ወደ ስራ እንዲገባ እና ልዩ ክትትል እንዲደረግለት” ውሳኔ ተላልፎ ነበር። ከንቲባ አዳነች በትላንቱ ገለጻቸው ይህንኑ አረጋግጠዋል።
“ይሄንን በምንሰራበት ሰዓት ከመንገድ ላይ የሚነሱ፣ ከመንገድ ላይ ወደ ውስጥ ጠጋ የሚሉ አጥሮች ይኖራሉ። ከተለያየ ቦታ ላይ በእርጅና አሁን ያለንበትን ዘመን የማይመጥኑ ግንባታዎች አሉ። ከከተማው መዋቅራዊ ፕላን ውጪ የተገነቡ አሉ። የተለያዩ ጥፋቶች አሉ...እርሱን ለማስተካከል ሰዎችን ከቦታቸው ልናነሳ እንችላለን” ሲሉም አዳነች ተናግረዋል።
"ፐርፐዝ ብላክ ለህንፃዉ ግብይቱ አስፈላጊውን ክፍያ ለመፈፀም የሚያስችል አቅም እንዳለው የሚያሳይ መረጃ ማቅረብ አልቻለም" ቢጂአይ ኢትዮጵያ ‼️
ቢጂአይ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ግብይቱን ለመፈፀም የሚያስችል አቅም የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ የሽያጭ ዉሉ እንዲሰረዝ ሆኗል ብሏል።
ከሰሞኑ በፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ እና በቢጂአይ መካከል ላለፉት 8 ወራት ሲደረግ የነበረዉ የዋና መስሪያቤት የሽያጭ ዉል ያለስምምነት ተቋጭቷል።
ግብይቱን ለመጨረስ እና የሽያጭ ዉሉን ለማሰር ከሚያስፈልገው ጊዜ በላይ በእጅጉ የተራዘመ ነበር ያለዉ ቢጂአይ ፐርፐዝ ብላክ በድጋሚ ድርድር ለማድረግ ያነሳዉ ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው አፅንኦት ሰጥቶበታል።
ከቀናት በፊት ከቢጂአይ ጋር የነበረዉ ዉሉ ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ ተቋርጧል ያለዉ ፐርፐዝ ብላክ ዉላችን በዉልና ማስረጃ መፅደቅ ሲገባዉ በቢጂአይ በኩል ይህ ሳይሆን ቀርቷል ሲል ወቀሳ አቅርቧል።
ይህን አስመልክቶ የቢጂአይ ኢትዮጵያ የህግ ክፍል ዳይሬክተር ነጋ ምህረቴ እንደተናገሩት በሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ላይ ከተደረሰዉ ሀሳብ በተለየ መልኩ ፐርፐዝ ብላክ በተቃራኒው አዳዲስና የመጀመሪያውን ስምምነት የሚቃረኑ ሃሳቦችን ይዞ ማቅረብን በማስታወስ ለድርጅቱ ይህን በተደጋጋሚ ቢያሳዉቅም ቁርጠኝነት ሊኖረዉ አልቻለም ብለዋል።
የሽያጭ ዉሉን ለመፈረም ፍቃደኝነቱን አላሳየም ያለዉ ቢጂአይ አሁን ላይ እያስኬድኩ እገኛለሁ ካለሁ 6 ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንደመፈለጋቸው ሂደቱ አላግባብ መራዘሙ ተፅዕኖ መፍጠሩን በመግለፅ ስምምነቱን አቋርጫለሁ ብሏል።
በድጋሚ የዋና መስሪያቤት ህንፃዉን ለመሸጥ ፍላት እንዳለዉ የገለፀው ቢጂአይ ይህም የተጀመረዉ የዉል ስምምነት ከተጠናቀቀ በኃላ ይሆናል ብሏል።
" እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ገንዘቡን ካልመለሱ ማንነታቸውን ለፖሊስ እናሳውቃለን - ንግድ ባንክ
የኢትዮጵያ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ከ " ቢቢሲ ኒውስ ዴይ " ጋር በነበራቸው ቆይታ ባንኩ የሲስተም ብልሽት ባጋጠመው ወቅት የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞች እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ገንዘቡን ካልመለሱ ማንነታቸውን ለፖሊስ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
" በዲጂታል ነው ዝውውር የፈጸሙት። ደንበኞቻችን ስለሆኑ እናውቃቸዋለን። " ያሉት የባንኩ ፕሬዜዳንት ፤ " የፈጸሙት ተግባር በሕግ ያስጠይቃቸዋል። ለፖሊስ ማንነታቸውን እናሳውቃለን " ብለዋል።
" አሶሼትድ ፕሬስ " ባንኩ አርብ መጋቢት 6 ለሊት የሲስተም ችግር በገጠመው ወቅት የተወሰደበት ገንዘብ 2.4 ቢሊዮን ብር (40 ሚሊዮን ዶላር) መሆኑን ዘግቧል።
ይህ ወጥቷል የተባለው ገንዘብ ትክክለኛ ነው ወይ ? ተብለው የተጠየቁት የባንኩ ፕሬዝዳንት ፤ " የኦዲት ምርመራው ባለመጠናቀቁ የተወሰደውን ገንዘብ መጠን አሁን ላይ አይታወቀም " ብለዋል።
" ገና ኦዲት እየተደረገ ነው። ዝውውሩ ውስብስብ ነው። ጤናማ የሆነ ዝውውር የፈጸሙ እንዳሉ ሁሉ፤ የሌላቸውን ገንዘብ ያወጡም አሉ። ስለዚህ ማጣራት ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል። ምናልባት በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንጭርሳለን ብለን እንጠብቃለን "ብለዋል።
አቶ አቤ ፤ 10 ሺህ የሚሆኑ ግለሰቦች የገንዘብ ዝውውር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አርብ ሌሊት ከ490 ሺህ በላይ " ጤናማ እና ጤናማ ያልሆኑ " የገንዘብ ዝውውሮች መከናወናቸውን መናገራቸው ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
#አጣዬ
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ ትናንት ጀምሮ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ከፍተኛ ተኩስ መኖሩን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል። ህዝቡም መውጫ አጥቶ ቤቱ ቁጭ ብሏል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት አጎራባች ከሆነው የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን የመጡ ታጣቂዎች ጭምር በተኩሱ ተሳታፊ ናቸው ብለዋል።
ተኩሱ በማን መካከል እየተካሄደ እንደሆነ ለማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
" የትግራይ ጡረተኞች ክፍያው እንዲፈፀምላቸው ተወስኗል " - ዶ/ር እዮብ ተካልኝ
በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት የጡረታ ገንዘብ ያልተከፈላቸው ጡረተኞች፤ በፖለቲካ ውሳኔ መሰረት ደሞዝ እንዲከፈላቸው መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታና የጡረታ ፈንድ የቦርድ አባል ዶክተር እዮብ ተካልኝ ማሳወቃቸውን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ዶ/ር እዮብ ፤ የጡረታ መዋጮ ባልተሰበሰበበት ሁኔታ ጡረታ እንዲከፈል የሚፈቅድ አሰራር አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ውሳኔው ፖለቲካዊ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በዚህም ከፕሪቶሪያው ስምምነት በፊት ክፍያ ተቋረጦባቸው የነበሩ ጡረተኞች፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት ክፍያ ይፈፀምላቸዋል ብለዋል። አሰራሩ በመንግስት ተቋማት እና በግል ድርጅቶች ይሰሩ የነበሩ ጡረተኞችን እንደሚመለከት ጠቁመዋል።
ከትግራይ ጡረተኞች ክፍያ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳ እንደነበር ጠረተኞችም ሰላማዊ ሰልፍ እስከመውጣት መድረሳቸው ይታወሳል።
ከቀናት በፊት ጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከትግራይ ክልል ከመጡ የህዝብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የጡረተኞች የደሞዝ ክፍያ አልተፈጸመም የሚል ቅሬታ ቀርቦ ነበር።
ጠ/ሚኒስትሩ ፤ " ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግሬ በአጭር ጊዜ ምላሽ ይሰጣል " የሚል ምላሽ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል።
በተደረሰው ፖለቲካዊ ውሳኔ በጦርነቱ ምክንያት ያለተከፈለ የጡረተኞች ደሞዝ ተሰልቶ ይከፈላቸዋል ተብሏል።
በሸዋሮቢት ከተማ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት ወታደሮች መካከል ግጭት ቀጥሏል
👉🏼 በሸዋሮቢት ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከተቋረጠም ከ 20 ቀናት በላይ እንደሆነ ሰምተናል
በሸዋሮቢት ከተማ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች ላይ አሁንም ግጭት ያለባቸው መኖራቸውን ከከተማዋ ነዋሪዎች ሰምቷል። ላለፉት አራት ቀናት በቆጥ፣ ሞላሌ እና ዋጮ ቀበሌ ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች ላይ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን እና የሰው ህይወት መጥፋቱንም ተገልጿል።
በሸዋሮቢት ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከተቋረጠ ከ 20 ቀናት በላይ እንደሆነ እና ከደብረብርሃን እንዲሁም ከደሴ ምንም አይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አለመኖሩንም ዳጉ ጆርናል ተረድቷል።
የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪዎችም ትራንስፖርት እንቅስቃሴ በመቋረጡ ምክንያት የኑሮ ውድነቱ መቋቋም አለመቻላቸውን እንዲሁም የስራ እንቅስቃሴዎች የተቋረጠባቸው መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ነዋሪዎችም ለአስፈላጊ ነገሮች ሲንቀሳቀሱ ሲኖትራክ እንዲሁም ተመሳሳይ ፍቃድ ያላቸውን የትራንስፖርት አገልግሎቶች እየተጠቀሙ እንደሆነ ይህም በቀላሉ የሚገኝ እድል አለመሆኑን አንስተዋል። በተጨማሪም ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በዚህም መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮችንም ወደ ከተማዋ ለማስገባት እና ለመንቀሳቀስ ከባድ እንደሆነባቸውም አንስተውልናል።
ነጋዴዎች ቀድመው ያስገቡትን እቃዎች በውድ ዋጋ በመሸጥ ላይ መሆናቸው የነገሩን ሲሆን በዚህም ሽንኩርት ኪሎ እስከ 135 ብር ፣ ቶማቲም 50 ብር፣ ስኳር በትንሹ አንድ ኪሎ ከ150 ብር ጀምሮ እየተሸጠ እንደሚገኝ ነግረውናል።
በመሆኑም የአካባቢው ነዋሪዎች በኑሮ ውድነቱ መማረራቸውን በከተማው ያለው የስራ እንቅስቃሴም መቀዛቀዙ እንዳሳሰባቸው እና ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነም ገልጸዋል ። ጉዳዩ በተመለከተ ዳጉ ጆርናል ምን ዓይነት መፍትሄ ሊሰጥ እንድታሰበ እና ትራንስፖርት እንቅስቃሴውን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ቢሞክርም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ከሁለት ወር በኋላ በአዲስ አበባ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ለሚያጫውቷቸው ሙዚቃዎች ክፍያ እንዲፈፅሙ ይገደዳሉ ተባለ
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች የላባችን ፍሬ ያሉትን የሮያሊቲ ክፍያ ለማስጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል::
የኢትዮጵያ የሙዚቃና የቅጂ መብቶች የጋራ አስተዳደር እና የሙዚቃ ዘርፍ ማህበር ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ እንዳለው ከሁለት ወር በኋላ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሮያሊቲ ክፍያን በፌደራል ደረጃ መሰብሰብ እንደሚጀምር የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም ከሆቴሎች (መዝናኛ ስፍረዎች) እና በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የሬዲዮና የቲቪ ጣቢያዎች ተግባራዊነቱ እንደሚታይ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ፦ የእለተ ሰኞ ኢትዮትዩብ አንኳር አጫጭር ዜናዎች - መጋቢት 9 ፣ 2016 | #Ethiopia: EthioTube Ankuar : አንኳር - Ethiopian Daily News Digest - March 18, 2024
👉 ንግድ ባንክ አዲስ የከፈተው ዘመቻ
👉ሰሞኑን በፀሀይ ዙሪያ እየተፈጠረ ያለው ምንድነው
👉 የፑቲን መመረጥ ያንገበገባቸው ሀገራት
ሌሎችንም መረጃዎች ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/Vl9R9A9RcTs
ወርቅና ብር ይዘው መውጣት አይችሉም ሲሉ የነበሩ ሰራተኞች በካሜራ እገዛ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ
ወርቅና ብር ይዘው መውጣት አይችሉም ሲሉ የነበሩት አካላት የጉምሩክ ክፍልን የሚመለከት እንደነበርና አሁን በካሜራ እገዛ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰሞኑን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከመንገደኞች አገልግሎት አሠጣጥ ጋር በተያያዘ ቅሬታ መቅረቡን ተከትሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በመግለጫቸው እንዳሉት እየተሰሙ ያሉ ቅሬታዎችን መርምሮ መፍትሄ ለመስጠት አየር መንገዱ በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ አገልግሎት ከሚሰጡ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ቅሬታዎችን የማጣራትና የእርምት እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህም ወርቅና ብር ይዘው መውጣት አይችሉም የተባሉት ደንበኛ ጉዳይ ዋነኛው ቅሬታ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ድርጊቱን የፈፀሙት የጉምሩክ ክፍልን የሚመለከት እንደነበር ገልጸው በመሆኑም ግለሰቦቹን በካሜራ እገዛ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል ብለዋል። አየር መንገዱ እንዲህ አይነት ድርጊቶችን የማይታገስ መሆኑንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡
በቀጣይ ቀናት የሙቀት መጠን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል የሚባለው መረጃ ሀሰት ነው-የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
በቀጣይ ቀናት የሙቀት መጠን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል የሚባለው መረጃ ሀሰት መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በቀጣይ ቀናት የሙቀት መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመርን ተከትሎ የአልትራ ቫዮለንት የጨረር መጠን ከፍ ይላል እየተባለ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው መረጃ ሀሰት ነው ሲሉ በኢንስቲትዩት የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ ለኢቢሲ ሳይበር ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የፀሀይ መጠን መጨመር እና አልትራ ቫዮለንት የተለያዩ ናቸው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
የፀሐይ ሙቀት መጨመር ማለት ከወትሮው ከሚስተዋለው በተለየ መጠኑ የጨመረ ሙቀት ማለት ሲሆን ፤ አልትራ ቫዮለንት አደገኛ የሆነ በሰው እና በእንስሳት ላይ ተፅዕኖ ሊያደርስ የሚችል ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
Facebook.com/EthioTube
Twitter.com/EthioTube
Youtube.com/EthioTube
Instagram.com/EthioTube
/channel/ethiotube
ንግድ ባንክ ፤ ባሳለፍነዉ አርብ ሌሊት ባጋጠመዉ ችግር 25 ሺ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር መደረጉና 2.6 ቢሊየን ብር መንቀሳቀሱ ተነገረ
👉🏼 ባንኩ ገንዘብ የወሰዱ ሰዎችን ለመጠየቅና ገንዘቡን ለማስመለስ ግብረሀይል ያቋቋመ ሲሆን በባንኩ ዲጂታል መዋቅር ላይ በውስጥ አዋቂ የተፈፀመ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ገምተዋል
ቅዳሜ ዕለት በየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል መዋቅር ላይ የተከሰተውን ግድፈት ተጠቅመው ገንዘብ የወስዱ አካላትን ለማደን ግብረ ኀይል መቋቋሙን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ሰምታለች።
ከብሔራዊ ባንክና ንግድ ባንክ ባለሙያዎች እንዲሁም የፀጥታ አካላት የተካተቱበት ይህ ግብረ ኀይል በስድስት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከባንኩ ያለ አግባብ ተወስዷል ያለውን ገንዘብ ለማመለስ ያለመ ነው። ባንኩ የተወሰደበትን የገንዘብ መጠን አላሳወቀም። ፎርቹን ጋዜጣ እንደዘገበው ግን ከ 66 ሺህ በላይ ደንበኞች አካውንት በችግሩ መታወኩን፣ ቅዳሜ ለስድስት ሰዓታት በቆየው መታወክ 25 ሺ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር መደረጉን እንዲሁም ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር ተንቀሳቅሷል። ሆኖም ባንኩ መረጃውን ማረጋገጥ አልፈለገም።
አንዳንድ የትምህርት ተቋማት ከወዲሁ ገንዘብ ከክፍያ ማሽኖች የወሰዱና በህገወጥ ዝውውሩ የተሳተፉ ተማሪዎች ገንዘቡን ለባንኩ እንዲመልሱና ራሳቸውን ከህግ ተጠየቂነት እንዲያተርፉ የሚያሳስብ ጥሪ ማስተላለፋቸዉን ዳጉ ጆርናል ዘግቧል። በባንኩ ላይ የደረሰው ችግር የሳይበር ጥቃት አለመሆኑንና ውስጣዊ ግድፈት መሆኑን ባንኩ አበክሮ ገልጿል።
የባንኩ የውስጥ ምንጮች ለዋዜማ እንደተናገሩት ግን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተከናወነ አንድ መንግስታዊ የባንክ ክፍያ (ከአንድ መቶ ሚሊየን ብር ያላነሰ) ከአንድ በላይ የከፋይ ወገን በዲጂታል ፊርማ ሊያፀድቀው ሲገባ በአንድ ሰው ፈራሚነት ወደ ተከፋይ መተላለፉን የባንኩን ሀላፊዎች አስደንግጦ ነበር። አርብ ዕለት ችግሩን ለማወቅና ለመፍታት ሙከራ ሲደረግ መዋሉንና የቅዳሜ ሌሊቱ ቀውስ መከተሉን ሰምተናል።
ባንኩ የሳይበር ጥቃት አለመፈፀሙን ይናገር እንጂ ክስተቱ በባንኩ ዲጂታል መዋቅር ላይ በውስጥ አዋቂ የተፈፀመ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ባንኩ ከተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰራተኞችን ከስራ ያሰናበተ መሆኑን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል።
ብሄራዊ ባንክ፣ ቅዳሜ እለት በንግድ ባንክ ላይ ያጋጠመው የአገልግሎት መቋረጥ በባንኩ አገልግሎት መስጫ ሥርዓት ላይ ከተደረገ የደኅንነት ፍተሻና የማሻሻያ ሥራ ጋር የተያያዘ እንደኾነ ገልጧል።
ብሄራዊ ባንክ፣ ክስተቱ የባንኩን፣ የደንበኞቹንና አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል አለመኾኑን አረጋግጫለኹ ብሏል። ባንኩ፣ ችግሩ ባስከተላቸው ጉዳቶች ላይ ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ወደፊት እንደሚገልጥ አስታውቋል። ባኹኑ ወቅት የኹሉም የፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ ሥርዓቶች ደኅንነቸው የተጠበቀ መኾኑን ባንኩ ገልጦ፣ ኅብረተሰቡ ያለ ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም እንዲቀጥል አሳስቧል።
ምንጭ ፦ ዋዜማ እና ፎርቹን
ኢትዮጵያ፦ የእለተ አርብ ኢትዮትዩብ አንኳር አጫጭር ዜናዎች - የካቲት 29 ፣ 2016 | #Ethiopia: EthioTube Ankuar : አንኳር - Ethiopian Daily News Digest - March 8, 2024
👉 የሊያ አዲሱ ስራ በአሜሪካ
👉የፒያሳ እና የአራት ኪሎ ነዋሪዎች ጉዳይ
👉 የትግራይ ባለሀብቶች የገጠማቸው ዱብ እዳ
ሌሎችንም መረጃዎች ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/DkzVFSgVJGM
የቀድሞ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የሀርቫርድ የሚኒስትሮች አመራር ፕሮግራምን በዳይሬክተርነት ተቀላቀሉ
በኮቪድ ወቅት በሳል አመራር በመስጠት የሚታወቁት ዶ/ር ሊያ የሀርቫርድ የሚኒስትሮች አመራር ፕሮግራምን በአሜሪካን ሀገር በሀላፊነት ደረጃ መቀላቀላቸው ታውቋል።
የዛሬ 12 አመት ገደማ የተቋቋመው ይህ ፕሮግራም በጤና፣ ፋይናንስ፣ ትምህርት እና ሌሎች ዘርፎች ለአፍሪካ፣ ደቡብ-ምስራቅ እስያ እና ላቲን አሜሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን እስካሁን ከ66 ሀገራት የተውጣጡ 262 ሚኒስትሮች ተሳትፈውበታል።
ዶ/ር ሊያ በሚኒስትርነት ወቅታቸው ከስራ ባልደረቦቻቸው ሆነ ከሚድያ ሰራተኞች ጋርም ተናበው በመስራት አርአያ የሆኑ ናቸው።
መልካም የስራ ዘመን ተመኝተናል
ጃፓን ሴቶች በወር አበባ ወቅት የሚሰማቸውን ህመም ወንዶች እንዲያውቁት የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ሰራች።
የዓለም ሴቶች ቀንን አስመልክቶ የጃፓን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሴቶች የወር አበባቸውን በሚያዩበት ወቅት የሚሰማቸውን የህመም ስሜት የሚያሳይ ቴክኖሎጂውን ይፋ አድርጓል።
በናራ የሴቶች ዩንቨርስቲ እና ኦሳካ በተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰራው ፔሮኖይድ የተሰኘው ይህ ቴክኖሎጂ በወንዶች ሆድ ላይ እንዲገጠም ተደርጎ በወር አበባ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ህመሞችን ያስተላልፋል።
ቴክኖሎጂው በወር አበባ ወቅት የሚደርሱ የሆድ ቁርጠት እና ተያያዥ ህመሞች ጋር አቻ የሆነ ህመምን እንደሚያስተላልፍም ተገልጿል።
በበጎ ፈቃደኛ ወንዶች ላይ የተሞከረው ይህ ቴክኖሎጂ ወንዶቹ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ህመሙ ከባድ እና የሚታገሱት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የ26 ዓመቱ ወንድ ወጣት እንዳለው በህመሙ ምክንያት መነሳት እና መራመድ አልቻልኩም ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።
ሴቶች በየወሩ በወር አበባ ወቅት ከህመማቸው ጋር እየታገሉ ስራ እንደሚሰሩ ወንዶች ሊያውቁ እና ህመማቸውን ሊረዱ ይገባልም ተብሏል።
በጃፓን ያሉ አሰሪ ተቋማት ሴቶች በወር አበባ ወቅት ፈቃድ የመውሰድ እና ክፍያ የማግኘት መብት የሚፈቅድ ህግ ቢኖርም ብዙ ሴቶች ግን ይህን መብት በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት አይጠቀሙትም ተብላል።
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ነው
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
ቀኑ “ሴቶችን እናብቃ፣ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ የሚገኘው፡፡
በመርሐ ግብሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) እና ሌሎች እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ለ113ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ ነው በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ የሚገኘው፡፡
ኢትዮጵያ፦ የእለተ ሀሙስ ኢትዮትዩብ አንኳር አጫጭር ዜናዎች - የካቲት 28 ፣ 2016 | #Ethiopia: EthioTube Ankuar : አንኳር - Ethiopian Daily News Digest - March 7, 2024
👉 ህውሃት ዳግም ወደ ጦርነት ስለመግባቱ የሰጠው ምላሽ
👉ሸኔ ወደ ሃዋሳ የሚሄደውን መንገድ ዘጋ
👉 የፐርፐዝ ብላክ የከሸፈ ስምምነት
ሌሎችንም መረጃዎች ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/AVFcIpjDoag
ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያዩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዛሬ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳሉት ÷ "መዲናችን ከከተማ መስፋፋት ጋር የሚመጣ ፍላጎትን የሚያጎሉ ወሳኝ የሆኑ የእድገት እና የለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች"።
የዛሬው ዓይነት ስብሰባዎች በሚታዩ ክፍተቶች የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ብሎም መልካም አጋጣሚዎችን ለመለየት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡