ኢትዪትዩብ፦ ኢትዮጵያዊ። ነፃ። ገለልተኛ። Follow us on other platforms: Facebook.com/EthioTube Twitter.com/EthioTube Youtube.com/EthioTube Instagram.com/EthioTube
የአንጋፋዋ ጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ የቀብር ሥነ ስርዓት ተፈጸመ
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ፕሮግራም ላይ ሰፊ አገልግሎት ከሰጡና ተጽኗቸው ከላቀ ጋዜጠኞች አንዷ የነበረችው ጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ የቀብር ሥነ ስርዓት ዛሬ በቤቴል ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
ዓይናለም ባልቻ ሐምሌ 21 ቀን 1961 ዓ.ም የተወለደች ሲሆን የልጅነት ጊዜዋን በህፃናት አምባ አሳልፋለች። የከፍተኛ ትምህርቷን በቡልጋሪያ ቀጥላ በጋዜጠኝነት ትምህርት በማስተርስ ተመርቃለች።
ጋዜጠኛ ዓይናለም በ1988 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን የተቀላቀለች ሲሆን በጣቢያው ለ25 ዓመት ያህል አገልግላለች። ከ25 ዓመት በተቋሙ የሥራ ቆይታዋ ውስጥም ረዥሙ የሆነውን የሥራ ክፍል ያሳለፈችበትን ማለትም 15 ዓመትን የሰራችበት የህፃናት ክፍልን ወደ መጨረሻ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሥራ ቆይታዋ እስከ ዳይሬክተር በመሆን አገልግላለች።
ጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ ባደረባት የጤና እክል ምክንያት ከሥራዋ ተገላ ለረጅም ዓመት በሕመም ቆይታ ነበር። ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የአዲስ ዓመት ፕሮግራም ለአንጋፋዋ ጋዜጠኛ ዓይናለም ይፋዊ የዕውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት አበርክቶላታል።
ጋዜጠኛ ዓይናለም ባልቻ የአንዲት ሴት ልጅ እናት እና የሁለት የልጅ ልጆች አያት ነበረች። ኢትዩትዩብ ለቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመድ መጽናናትን ይመኛል።
ተፈናቃዮች ሳንፈልግ ሸሽተነው ወደመጣነው ቦታ ተመለሱ እየተባልን ነው አሉ።
ተፈናቃዮቹ ለደህንነታችን ዋስትና የለንም ቢሉም መንግስት በግዳጅ የሚመለስ ተፈናቃይ የለም ይላል።
በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ምዕራባዊ የወለጋ ዞኖች በተለያየ ጊዜያት ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች የሚገኙ ሰላማዊያያን ናቸው በግዳጅ ተመለሱ እየተባልን ነው ያሉት። ተፈናቃዮቹ ለልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ የብዙሃን መገናኛዎች እንደተናገሩት ጥለዋቸው ወደመጡት የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ከስጋት አንፃር የመመለስ ፍላጎት የላቸውም፤ ይሁንና በአጭር ጊዜ ውስጥ መመለሳቸው እንደማይቀር የአካባቢው ሹማምንነት ነግረዋቸዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ፅህፈት ቤት ተፈናቃዮቹን ወደቀያቸው የመመለስ ስራ የሚከናወነው በፈቃድ ላይ ተመስርቶ መሆኑን እና ተፈናቃዮቹ የሚመለሱትን የፀጥታ ሁኔታቸው አስተማማኝ ወደሆኑ አካባቢዎች መሆኑን ይሞግታል።
ጉዞው በዚህ ሳምንት መባቻ ላይ እንደሚጀምር እንደተነገራቸው የገለፁት ተፈናቃዮች ወደተፈናቀሉባቸው አካባቢዎችን መመለስን አስፈሪ የሚያደርግባቸው በክልሉ ምዕራባዊ ክፍሎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ የማያስተማምን እና የማይገመት በመሆኑ ነው።
ባሉባቸው የጊዜያዊ ማቆያዎች በቂ ድጋፍ እያገኙ ያለመሆኑን የሚናገሩት እነዚሁ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለስ የማይፈለጉ ከሆነ ከማቆያዎቹ በግዳጅ እንዲወጡ ሊደረጉ እንደሚችሉ ፍርሃት ገብቷቸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተናቃዮችን ቁጥር አስተናግዳለች።
በቅርብ ይፋ የሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በአሁኑ ጊዜ ከአራት ሚሊዮን የሚልቁ ተፈናቃዮች በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች በጊዜያዊ ማቆያ ጣብያዎች ይገኛሉ። ይህም አገሪቷን ከፍተኛ የተፈናቃዮች ቁጥር ካለባቸው የአፍሪካ አገራት ተርታ ያስቀምጣታል። ግጭቶች ዋነኛ የመፈናቀል ምክንያት ሆነው ቀጥለዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት ከተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ የሚሰጧቸው መፍትሔዎች በአብዛኛው ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው መመለስ ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ ይህ ግን በተለይ የማንነት ተኮር ጥቃቶች ሰላባዎች በሆኑ እንዲሁም በግጭቶች ምክንያት ቤት አልባ በሆኑ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ሲያገኝ አይስተዋልም።
ኤርትራ ከያዘቻቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ለቅቃ ትውጣ ሲል የእውሮፓ ኅብረት ያወጣውን መገለጫ “የለየለት ቅጥፈት” ስትል አጣጣለች።
የአገሪቱ የመረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ ወኪሎች ወደኢትዮጵያው ትግራይ ክልል በማቅናት የኤርትራ ጦር በክልሉ እንዳለ በመግለፅ የለየለት ቅጥፈትን እንደበቀቀን አነብንበዋል ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል። እንዲህ ዓይነት የአውሮፓ ኅብረት ውንከላ የተለመደ እየሆነ መጥቷል ሲሉ የመረጃ ሚኒስትሩ አክለው በፅሁፋቸው አትተዋል።
የማነ ይህን ያሉት ሰሜናዊውን የኢትዮጵያ ክልል ትግራይን የጎበኙ የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ ልዑካን የኤርትራ ጦር ከያዛቸው የትግራይ አካባቢዎች ለቅቆ መውጣት አለበት ማለቱን ክልላዊው ቴሌቭዥን ከዘገበ በኋላ ነው።
የኤርትራ ጦር በሁለት ዓመቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ፌዴራላዊውን መንግስት ወግኖ ስለመሳተፉ ብዙ የተዘገበ ሲሆን በወቅቱም የመብት ጥሰቶችን ፈፅሟል ተብሎ ተወንጅሏል። ይሁናን ለጦርነቱ መቆም ምክንያት የሆነው የሰላም ስምምነት ሲደረግ በውይይቱ ያልተካተተ ሲሆን እስካሁንም የያዛቸው አካባቢዎች አሉ እየተባለ ይታማል። ይሁንና አስመራ ይሄንን መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ስትል ታጣጥለዋለች።
መንግስት ከአንድ ሺህ አምስት መቶ የሚልቁ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት ወደሰላማዊ ህይወት ተመልሱ አለ።
መንግስት “ሸኔ” እያለ የሚጠራውና በኢትዮጵያ ህግ በሽብርተኛነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጥ አልተሰማም።
የታጣቂ ቡድኑ አባላት ስልጠና ወስደው ወደሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን ነው ለመንግስት ቀረብ የሚሉ የብዙሃን መገናኛዎች የዘገቡት።
አስቸኳይ አዋጅ ጋር በተገናኘ ታስረው የነበሩ በርካታ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ወደኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል ተብሎ መዘገቡ ይታወሳል።
ስልጠናቸውን ጨርሰዋል የተባሉት የኦሮሚያ ታጣቂዎች ቃለ መሃላ የፈፀሙ ሲሆን የይቅርታ መርኃ ግብርም ተከናውኖላቸዋል ተብሏል። የይቅርታ እና የቃለ መሃላ ስርዓቱ የተፈፀመው በቢሻን ጉራቻ ከተማ በሚገኝ ቶጋ የተሰኘ ካምፕ መሆኑም አብሮ ተዘግቧል። ሰልጣኞቹ በቃዳቸው እጃቸውን ለመንግስት የሰጡ እና የተማረኩ ናቸውም ተብሏል። የመንግስት የብዙሃን መገናኛዎች ሰልጣኞቹ ወደትጥቅ እንቅስቃሴ የገቡት በስህተት መሆኑን አምነው በጥፋታቸው እንደተፀፀቱ፥ ዳግመኛም በተመሳሳይ ተግባር ላለመሳተፍ ቃል እንደገቡ ተናግረዋል።
በመንግስት እና በታጣቂው ቡድን መካከል በሁለት ዙር ድርድር በምስራቅ አፍሪካዊቷ ታንዛኒያ ሲከናወን የነበረ ሲሆን ድርድሩ ያለውጤት መበተኑ አይዘነጋም። በተለይ ከሁለተኛው ዙር ድርድር ያለውጤት መበተን በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል ቃላት መወራወር በርትቶ ተስተውሏል። ከእርሱም ባሻገር ግጭቶች በኦሮሚያ ጠንከር ብለው የታዩ ሲሆን በሰላማዊ ዜጎች ላይም ጥቃቶች ተመዝግበዋል።
ሌላ ዙር ድርድር ሊኖር የመቻል እድል እንዳልተሟጠጠ በቅርቡ ዘለግ ያለ ቃለ መጠይቅ የሰጡት የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጠቆም ማድረጋቸው ይታወሳል።
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት በተባለች ከተማ እና በአቅራቢያዋ ከሰሞኑ ከፍተኛ የሚባል የተኩስ ልውውጥ በታጣቂዎች እና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መካከል መደረጉ ተዘገበ።
በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ከሰሞኑ ለታጠቂዎች የቀረበውን በሰላም ግቡ ጥያቄ በርካቶች እየተቀበሉ ነው ብሏል።
ቢያንስ ለሁለት ቀናት የዘለቀው የፈረስ ቤት ውጊያ ከፍተኛ የሚባል እንደነበር ከነዋሪዎች ሰምቻለሁ ሲል ዘገባ ያሰራጨው የጀርመን ድምፅ የአማርኛ አገልግሎት የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋን ይዘዋት እንደነበርም ጨምሮ ገልጿል። የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከተማዋን ለማስለቀቅ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍቶ ነበርም ሲሉ ነዋሪዎች መናገራቸውን የሬዲዮ ጣብያው ዘገባ ያመላክታል። ውጊያው በከባድ መሳርያዎች የታገዘ ሲሆን ይህም ለነዋሪዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳስን አዳጋች አድርጎታል። ይሁንና በውጊያው ስለደረሰ ጉዳት እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች ስለገጠማቸው ዕጣ ብዙም የተባለ ነገር የለም።
በአማራ ክልል የፀጥታ መደፍረስን ለማሻሻል ያግዛል በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ወደአምስት ወር እየተጠጋ ቢሆንም አሁንም ውጊያዎች እና ጥቃቶች መዘገባቸውን ቀጥለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግስታት ለንፁሃን ዜጎች ከለላ እንዲደረግ ሲማፀኑ ቢቆዩም በተለይ ሰው ሰብሰብ ብሎ በሚኖርባቸው ከተሞች አካባቢዎች የሚደረጉ ፍልሚያዎች ስጋት መጋረጣቸውን ቀጥለዋል። ከዚህ ቀደም የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዐዊ መብቶች ፅህፈት ቤት በአማራ ክልል ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ በሰላማዊ አካባቢዎች ላይ ያነጣጠሩ የድሮን ጥቃቶች እንዲሁም የመኖሪያ ስፍራዎች ላይ ያረፉ የከባድ መሳርያዎች የንፁሃንን ነብስ እየቀጠፉ ነው ሲል መናገሩ ይታወሳል። በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ወራት የተቆጠሩ መሆናቸው በምስል የተደገፉ እና ዘርዘር ያሉ መረጃዎችን ማግኘትን አዳጋች አድርጎታል።
የክልሉ መንግስት እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጠቅላይ መምሪያ በበርካታ አካባቢዎች በአንፃራዊነት የተሻለ የፀጥታ መሻሻል መኖሩን ይናገራሉ፤ ይሁን እንጅ አለ ከተባለው መሻሻል ጋር ተያይዞ አዋጁ ይነሳ ስለመሆኑ እንዲሁም የኢንተርነት አገልግሎት ስለመመለሱ ብዙም ሲናገሩ አይደመጡም።
በቅርቡ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሰላም ተመልሱና ወደማኅበረሰቡ ተቀላቀሉ የሚል ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን መጀመሪያ ለሰባት ቀናት ያህል ቀርቦ የነበረው ጥሪ ለተጨማሪ ቀናት እንደተራዘመም ተገልጿል። ይህንን ተከትሎ በርካቶች የትጥቅ እንቅስቃሴን ይቅርብን ብለው ወደሰላም እየተመለሱ ነው ብሏል የክልሉ መንግስት። የአማራ ክልል የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው በዚህ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ ጥሪ ተቀብለው ተመልሰዋል ያሏቸውን ታጣቂዎች ቁጥር ከአምስት ሺህ የሚበልጥ ነው ብለዋል። ሕዝቡ ለሰላም ጥሪው ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ወደሰላም ለመጡት ታጣቂዎች የመከላከያ ሠራዊት ጥበቃ እያደረገ ነው ያሉት የክልሉ ቃል አቀባይ ታጣቂዎቹን ለማስገባት ስራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን የመንግስት የብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል። ይሁንና እርሳቸው ያቀረቡትን ቁጥር በተመለከተ ከገለልተኛ ወገን የተገኘ ማረጋገጫ የለም።
የአርሶ አደሮች ምርታማነት እና የምጣኔ ኃብታዊ ተፎካካሪነት እንዲኖር ለሰላም ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል ሲሉ ቃል አቀባዩ አሳስበዋል።
በተያያዘ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በሚገመግም አንድ መድረክ ላይ ተገኝተው “አንፃራዊ ሰላም” እንዳለ እና ያንን በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። የሰላም ጥሪ ከቀረበ በኋላ “በርካቶች” ሲሉ የገለጿቸው ታጣቂዎች ወደሰላም መጥተዋል ሲሉ ተናግረው እነርሱን እያሰለጠንን ወደማኅበረሰብ እንመልሳለን ሲሉ ተደምጠዋል።
የክልሉ ሹማምንት እንደዚህ ይበሉ እንጅ አሁንም ግጭቶች መደመጣቸው አልቀረም። የውጭ አገራት ለዜጎቻቸው በሚያወጧቸው ማሳሰቢያዎች ክልሉ አሁንም ግጭት ማስተናገዱን መቀጠሉን እየጠቀሱ ከጉዞ እንደቆጠቡ ያስጠነቅቃሉ።
በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ወጥነው የነበሩ የውጭ አገር ኩባንያዎች ፍላጎት ተቀዛቅዟል ተባለ።
ለዚህም አንዱ ምክንያት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውና ብቸኛው የግል የቴሌኮም ኩባንያ የሆነው ሳፋሪኮም ወደሥራ ለመሰማራት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ የገጠሙት ተግዳሮቶች እና ውጣ ውረዶች ናቸው ተብሏል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የዘርፉን ባለሞያዎች አነጋግሬ እንደተረዳሁት ፈተና ሆነው ከታዩት ጉዳዮች መካከል የህግ ማሻሻያዎች፥ በአገሪቱ የሚታዩት የፀጥታ ችግሮች እንዲሁም ለአስርት ዓመታት ያህል በከፍተኛ ሁኔታ ተጠንቅሮ የቆየውን ዘርፍ በመክፈት ረገድ መንግስት የታሰበውን ያህል ትጋት ያለማሳየቱ ይገኙባቸዋል ብሏል።
ይህም መቶ ሃያ ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ይዛ ከፍተኛ የገበያ እምቅ አቅም አላት በሚል የቴሌኮም ዘርፍ ኩባንያዎች በከፍተኛ ፍላጎት ሲመኟት የነበረችውን ኢትዮጵያ ገበያ አሁን ደፍሮ ለመግባት ብዙም ተነሳሽነት የለም ሲል ዘገባው አክሏል።
ስለገጠሙት ውጣውረዶች ብጠይቀውም ሳፋሪኮም ኢትየጵያ ምላሽ አልሰጠኝም ያለው ሮይተርስ በዘርፉ ላይ ጥናት ሰርተው መፅሐፍ ያሳተሙ አንድ ባለሞያ ግን የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለው ነገር ውዥንብር የሚፈጥር ነው ብለውኛል ብሏል። “የኢትዮጵያ መንግስት ምን እያደረገ እንዳለ እርግጠኛ መሆን አይቻልም” ሲሉ ምሁሩ ነግረውኛል ያለው ሮይተርስ አንድ ጊዜ ገበያውን ሲከፋፍት ይታይና ወዲያው ደግሞ ሁሉንም ነገር መልሶ ይወስዳል ሲሉ ኃሳባቸውን ገልፀዋል ብሏል።
መንግስት በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየት እንደሌለ ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው ኦሬንጅ የተባለ የቴሌኮም ኩባንያ የመንግስታዊውን ኢትዮቴሌኮም አርባ አምስት በመቶ ድርሻ ልገዛ አስቤ የነበረውን ትቼዋለሁ ሲል ራሱን ማግለሉን መግለፁ ይታወሳል።
ሠራተኞቼ በፀጥታ ኃይሎች ተደብድበዋል ያለው የአፍሪካ የልማት ባንክ የውጭ አገር ባለሞያዎቹን ከኢትዮጵያ ጠቅልሎ ለማስወጣት ወሰነ።
ለሰራተኞቼ ደህንነት ዋስተና መተማመኛ የለኝም ሲል ገልጿል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሁለት የውጭ አገር ሠራተኞቼ በፀጥታ ኃይሎች ተወስደው ታስረዋል፥ ያላግባብ ተዋክበዋል እንዲሁም አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ያለው ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ደጋፊዎች መካከል አንዱ የሆነው የአፍሪካ ልማት ባንክ ክስተቱን እንደ ዲፕሎማሲያዊ ጥሰት እንደሚቆጥረው ገልፆ ነበር።
ምንም እንኳ በወቅቱ ባንኩ ታሰሩና ተደበደቡ የተባሉ የውጭ አገር ሰራተኞቹን ማንነት ገልፆ ያልነበረ ቢሆንም የተለያዩ ዘገባዎች ግን የባንኩን የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ እንደሚጨምር ገልፀው ነበር።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የወቅቱ መግለጫ ሰዎቹን ከእስር ማስፈታት የቻለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ንግግር በማድረግ እንደሆነም ተናግሮ ነበር።
አሁን ከባንኩ ፕሬዚዳንት እና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወዳጅ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው ከናይጄሪያዊው ከአኪናዋ አዴሲና የተፃፈ መመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የባንኩ የውጭ አገር ሠራተኞች ጓዛቸውን ጠቅልለው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። የባንኩ ተቀጣሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ግን እዚሁ ይቀራሉ፤ ከሥራ ገበታቸውም አይቀነሱም ይላል ይሄው መልዕክት።
ከሳምንታት በፊት የተከሰተውን ጥቃት ተከትሎ በባንኩ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደአዲስ አበባ ልከን የኢትዮጵያ ሹማምንትን እንዲሁም የባንኩን ሠራተኞች አነጋግረን ነበር ያለው የአፍሪካ ልማት ባንክ በግምገማችን የደረስንበት ድምዳሜ ጉዳዩ አጥጋቢ በሆነ መልኩ እንዳልተፈታ፥ ሠራተኞቻችን በልበ ሙሉነት ደህንነት ተስምቷቸው ስራቸውን ለመከወን እንዲሁም ከቦታ ቦታ ምንም ትንኮሳ ሳይደርስባቸው ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ ገብቶናል ብሏል።
በወቅቱ ከተፈፀመውና “እጅግ የከፋ ጥሰት” ካለው ክስተት ጋር በተገናኘ የፀጥታ ኃይሎች እያደረግን ነው ያሉትን ምርመራ ውጤት እስካሁንም አላሳወቁንም ያለው ባንኩ የሠራተኞቼን ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም መብታቸውን ለማስከበረ የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም ሲል ተናግሯል።
የአፍሪካ የልማት ባንክ ኢትየጵያ ውስጥ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ስምንት ፕሮጄክቶች ያሉት ሲሆን የውጭ አገር ባለሞያዎቹን ጠቅልሎ በማስወጣቱ ስራዎቹ ላይ ሊኖር ስለሚችል መስተጓጎል ምንም ያለው ነገር የለም።
መንግስት በወቅቱ በክስተቱ ማዘኑን ገልፆ ምርመራም እንደሚደርግ ቃል ገብቶ የነበረ ሲሆን ከአሁኑ የባንኩ ውሳኔ ጋር ተያይዞ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።
ድንቅ መልዕክት !
እውነቱን ለመናገር እኛ ሀገር ውድ መኪና ለመንዳት ሞራሉም አይመጣልህም ፤ ከቤት ወትተህ የሆነ ቦታ ደርሰህ ስትመለስ መንገድ ላይ ስንት የተቸገረ ታያለህ መሰለህ ፤ ቤት አጥቶ መንገድ ዳር የተኛ ታያለህ ፤ የሚበላው አጥቶ የሚለምን ታያለህ ፤ ይህን እየተመለከትክ ውድ መኪኖች አሉኝ ብለህ እዚህ ህዝብ ላይ እራስህን ለማሳየት መሞከር በዚህ ህዝብ ላይ ራስህን መቆለል ምን ያደርጋል ? ፤ ምን ይባላል መሰለህ ‹‹ ብዙ ደሃ ባለበት ሀገር ውስጥ ሁሉም ሀብታም ደሃ ነው ›› ስለዚህ ማን ላይ ነው ራስህን የምታሳየው ? ፤ ውድ መኪና እየነዳህ ውድ ልብስ ለብሰህ ራስህን የምትቆልለው ፤ ያንተው ህዝብ ናቸው ወንድም እህትህ ናቸው ፤ የተቸገረ ህዝብ ላይ ራስህን መቆለል ትክክል አይደለም ፡፡
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ
ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያዊያንን ወደግዛቴ በህገ ወጥ መልኩ አስገብቷል ያለችውን የጭነት መኪና ሾፌር ቀጣች።
በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ ግዛት ባለች ምባቶ የተሰኘች ከተማ ያለ ፍርድ ቤት ነው የ39 ዓመት ዕድሜ አለው የተባለውን የጭነት መኪና ሾፌር የገንዘብ ቅጣት ያከናነበው።
ሾፌሩ በጭነት መኪናው ወደአገሪቷ ያስገባቸው ኢትዮጵያውያን በቁጥር አስራ ስምንት ሲሆኑ ዕድሜያቸውም በአስራ ስምንት እና በሃያ የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል። በአገሪቱ የሚታተሙ ጋዜጦች እንደዘገቡት ኢትዮጵያውያኑ ተገቢ ሰነዶች የሌሏቸው ሲሆን በመኪናው የዕቃ መጫኛ ክፍል ታጉረው ተገኝተዋል ተብሏል።
ሾፈሩ ኢትዮጵያውያኑን የያዘው ከዛምቢያዋ መዲና ሉሳካ አንስቶ ወደንግድ ከተማዋ ጆንሃንሰበርግ ሊያደርሳቸው በመጓዝ ላይ እያለ ነው በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው።
ኢትዮጵያኑ በጆሃንስበርግ ከተማ ያሉ ዘመዶቻችን ስራ እንፈልግላችኋለን ብለውን ነው ወደዚያው የምናቀናው ማለታቸውም አብሮ ተዘግቧል።
የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የትግራይ እና የአማራ ክልል ቀውሶች አሳስበውኛል አሉ።
ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴድሮስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘጋቢ ጋዜጠኞች ማኅበር ፊት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ነው የሁለቱን ክልሎች ሁኔታ ያነሱት። በትግራይ ክልል የሰላም ስምምነት ተደርጎ ጦርነት ቢቆምም የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች ቀጥለዋል ያሉት ቴድሮስ በክልሉ ከጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈፀሙ ፆታዊ ጥቃት ሰለባዎች ፍትሕ ያለማግኘታቸው አስቆጭ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እና ታዳጊዎች በጦርነቱ ወቅት ፆታዊ ጥቃቶች እንደተፈፀመባቸው የተለያዩ ዘገባዎች ያመላክታሉ። በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት የጥቃት ሰላባ የሆኑ ሴቶች ቁጥር ቀድሞ ከታሰበውም እጅጉን የላቀ ሳይሆን እንደማይቀር ማመላከቱ ይታወሳል።
ከጥቃቶቹ እንዲሁም ከሌሎች ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተገናኘ ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እንደሚከናወን ቃል ሲገባ የሚደመጥ ሲሆን እስካሁም ፆታዊ ጥቃትን ፈፅመዋል በሚል ፍርድ ቤት የቀረቡ ተጠርጣሪዎች ስለመኖራቸው በይፋ የተገለፀ ነገር የለም።
በክልሉ የተፈፀመው ፆታዊ ጥቃት ብዛት እጅጉን ሰቅጣጭ ነበር ያሉት ዶክተር ቴድሮስ በሙያ ሕይወታቸው በዚህ ልክ የደረሰ ጥቃት እንደማያውቁም ጨምረው ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ በቂ የብዙሃን መገናኛዎች ዘገባ ያለመኖሩ እንደሚያሳዝናቸውም አልደበቁም። የፆታ ጥቃት ሰለባዎች ተገቢ የሆነ የህክምና ድጋፍ የማግኘት መብት አላቸውም ሲሉ ተደምጠዋል።
ሬፊውጂ አንተርናሽናል የተባለ በስደተኞች ላይ የሚሰራ ተቋማ በትግራይ ካሉ ሴቶች ምናልባትም ከአርባ እስከ ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት አንዳች ዓይነት የፆታ ጥቃት እንደደረሰባቸው ጥናትን በማጣቀስ ፅፎ ሳነብ ልቤ ተሰብሮ ነበር ያሉት ዶክተር ቴድሮስ ትግራይ ሆነ ኮንጎ፥ ሄይቲ ሆነ እስራዔል ወይም ሱዳን አስገድዶ መድፈርን እንደጦር መሳርያ መጠቀም ዘግናኝ እና በሰብዐዊነት ላይ የተለደፈ ቆሻሻነት ነው ብለዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በአማራ ክልል ለወራት ያህል የቀጠለው ግጭት የጤና ተቋማት ላይ ጉዳት አድርሷል ሲሉ በዚሁ መድረክ ላይ የገለፁ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ አምቡላንስ በድሮን ተደብድቦ አምስት ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር በሁለቱ ክልሎች አስከፊ ድርቅ ተከስቶ ቀድሞም የነበረውን የምግብ እጥረት አባብሶታል፤ እናም አሁን ሚሊዮኖች ረሃብ ተጋርጦባቸዋል ብለዋል።
ዶክተር ቴድሮስ ዘለግ ባለው ንግግራቸው ከኢትዮጵያም ባሻገር ጋዛን፥ ምስራቅ ኮንጎን እንዲሁም ሱዳንን በማንሳት ትልቅ የጤና ዘርፍ ቀውስ በግጭቶች ምክንያት ተከስቷል ብለዋል።
ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሾሙ
ባለፈው ክረምት መልቀቂያ ያስገቡትም የቀድሞዋን ዳኛ እና የተቃውሞ ፖለቲካ መሪ ብርቱካን ሚደቅሳን ለመተካት ሰብሳቢ ሲያፈላልግ የከረመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉን ሾሟል። ሹመቱ ላይ ተወያይቶ እንዲያፅድቅ የቀበረለት የታችኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ሹመታቸውን አፅድቆላቸዋል። የሜላተወርቅ የአንድ ሰው ድምፀ ተዐቅቦ ብቻ ገጥሞታል።
በመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የትምህርት እና የሥራ ተሞክሯቸው በምክር ቤቱ የተነገረላቸው ሜላተወርቅ በቦርዱ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩ ባለሞያ ሲሆኑ ለሦስት ዓመታት ያህል የቦርዱ የፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ሜላተወርቅ በምክር ቤቱ ተገኝተው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ ልዑካን በሻንጋይ ከተማ የስራ ጉብኝት አደረገ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ የቻይና የንግድ ማዕከል በሆነችው በሻንጋይ ከተማ የስራ ጉብኝት እና ውይይት አድርገዋል፡፡
ልኡካን ቡድኑ በጉብኝቱ ዘመናዊ የከተማ መዋቅራዊ ፕላን እና አተገባበር፣ በመሰረተ ልማት ቅንጅትና ግንባታ ፣ በመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር እንዲሁም ዘመናዊ ከተማ አገነባብ ዙሪያ ከሻንጋይ ከተማ ፕላን እና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አመራሮች ጋር ውይይትና ጉብኝት አድርገዋል::
የሻንጋይ ከተማ በምትታወቅበት ዲጂታላይዝድ አገልግሎቶች እና በስማርት ሲቲ ግንባታ ሂደት ለሃገራችን ከተሞች ልምድ በምታጋራበት እና አብሮ መስራት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ከአዲስ አበባ አስተዳድ ከንቲባ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል::
በጉብኝቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ፣ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ፣ የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ጎሹ እንዳለማው፣ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ መኩሪያ መርሻዬ እንዲሁም ሌሎች የፌደራልና የከተሞች ባለሙያዎች መሳተፋቸውን መረጃው ጨምሮ ገልጿል::
በድርቅ ክፉኛ የተጎዳው የዋግ ኸምራ ዞን አስር ሚሊዮን ብር ገደማ የሚያወጣ ድጋፍ አገኘ።
በአማራ ክልል የሚገኘውና ከትግራይ የሚጎራበተው የዋግ ኸምራ ዞን ከተለያዩ ድጋፍ ሰጭዎች የተገኘ የምግብ እና የሌሎችም ቁሳቁሶች እርዳታ ደርሶታል። ድጋፉን ያስተባበረው የዋግ ኸምራ የልማት ማኅበር ሲሆን ከገንዘብ ደጓሚዎቹ መካከልም የአማራ ባንክ እና የመቄዶንያ የተራድዖ ድርጅት ይገኙበታል።
ድርቅ እጅጉን ከደቆሳቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል በርካታ የትግራይ ዞኖች እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኙት የዋግ ኸምራ እና የሰሜን ጎንደር ዞኖች ይገኙባቸዋል። በትግራይ ከድርቅ ጋር በተገናኘ በተፈጠረ የምግብ እጥረት እንዲሁም የምግብ እርዳታ በዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች ከመቋረጡ ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት የሚናገሩ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ወራት በዚሁ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር ከአንድ ሺህ ያስበልጡታል። በሰሜን ጎንደር እና በዋግ ኸምራ በአስርት የሚቆጠሩ ሰዎች በቅርቡ ህይወታቸው አልፏል ተብሏል። ከዚህም በላይ በሺህ የሚቆጠሩ ከብቶች ሞተዋልም ሲሉ ሹማምንት ይናገራሉ።
የዋግ ኸምራ ዞን አስቸኳይ ድጋፍ የማላገኝ ከሆነ ከፍተኛ ጥፋት ተጋርጦብኛል ሲል የአግዙኝ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን ዞኑ ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀሰው የልማት ማኅበር ጥሪውን መቀበሉን በተግባር አሳይቷል።
በዞኑ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከአንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ይልቃል። በዞኑ የሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በደረሰ ደረጃ ነዋሪዎቻቸው እርዳታን የሚጠብቁ ሲሆን ድርቁ ተማሪዎችንም ከትምህርት ገበታ ማራራቁ ይዘገባል።
በኢትዮጵያ አንዳንድ ቦታዎች ለአራት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በበቂ ሁኔታ ባለመዝነቡ እርዳታ ፈላጊዎች በዝተዋል፤ ድርቁ በምስራቅ አፍሪካ የታየው በአስርት ዓመታት ያልታየ የዝናብ እጥረት አካል ነው።
ሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች በአንፃሩ ያለወቅቱ የመጣ ዝናብ መብዛት እንዲሁም ከእርሱም ጋር የተያያዘ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት በርካቶች መፈናቀላቸው ይታወቃል። ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት በምስራቃዊው ሶማሊ ክልል ሰዎችን መግደላቸውም ይታወሳል።
በትግራይ ሽረ እንዳስላሰ መምህራን ከአንድ ዓመት ለሚልቅ ጊዜ ያልከፈላቸውን ውዝፍ ደምወዝ በመጠየቅ አደባባይ ወጡ።
መምህራኑ ከዚህም በተጨማሪ የግብር ቅነሳ እና የብድር ወለድ ስረዛን ጠይቀዋል።
በትግራይ ጦርነት በተፋፋመባቸው ሁለት ዓመታት በርከት ላሉ ወራት በተለይ የመንግስት ተቀጣሪዎች ደምወዝ እንዳላገኙ ሲገለፅ የነበረ ሲሆን ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ነገሮች ቀስ ቀስ ወደነበሩበት መመለስ ከጀመሩም በኋላ ያለፈ ክፍያቸውን እንዳላገኙ በመናገር ቅሬታ የሚያሰሙ ብዙሃን ናቸው።
በሽረ እንዳስላሰ ከተማ ለሰልፍ አደባበይ የወጡት መምህራን ቅሬታችንን ስሙ ካሉ ተቀጣሪዎች መካከል ይገኙባቸዋል። መምህራኑ የ2014 እና የ2015 ደምወዞቻችን ይከፈሉን፥ የግብር ዕዳ ይቃለልን፥ ከደደቢት ማይክሮፋይናንስ የወሰድነው ብድር ወለዱ ይሰረዝልን እና የመሳሰሉት ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ይዘው ነው ለሰልፍ የወጡት።
የችግሮች መደራረብ ኑሯችንን አዳጋች አድርጎታል ሲሉ ምሬታቸውን ያሰሙት መምህራኑ የሚመለከታቸው አካላት መላ ሊሰጡን ይገባል ብለዋል ሲል ክልላዊው ትግራይ ቴሌቭዥን ዘግቧል።
የመምህራኑን ማኅበር በበላይነት የሚመሩት ተክላይ በላይ መምህራኑ ትግራይ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ሰለባ ናቸው ብለዋል ሲል የቴሌቭዥን ጣብያው ጨምሮ ዘግቧል።
በትግራይ የጦርነት መቆም የሚሊዮኖችን ሰቆቃ እጅጉን መቀነሱ የሚታወቅ ቢሆንም በክልሉ ከጦርነት ጠባሳዎች እንዲሁም ከአስከፊ ድርቅ ጋር በተገናኘ ብዙሃን የከፋ ህይወት ውስጥ እንደሚገኝ ይዘገባል። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በክልሉ ያሉ ሲሆን ከድርቅ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የምግብ እጥረት ቁጥራቸው እያደገ ያለ ነዋሪዎችን ህይወት እየቀጠፈ ነው።
የክልሉ ምጣኔ ኃብት ከማገገም ብዙ ርቆ የሚገኝ ሲሆን በጦርነት የወደሙ በርካታ መሠረተ ልማቶችም ገና ዳግም አልተገነቡም። ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ከወደሙ መሠረተ ልማቶች መካከል ትምህርት ቤቶች ይገኙባቸዋል። ይህም የመማር ማስተማር ሒደትን ሙሉ በሙሉ ለማስቀጠል እንዳይቻል እንቅፋት ከፈጠሩ ምክንያቶች መካከል አንደኛው ሆኗል።
መምህራን እንደበርካታው የክልሉ ነዋሪ ከጦርነቱ ጥላ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት በአስከፊ የምጣኔ ኃብት እውነታዎች ተተብትቧል።
የትግራይ ቴሌቭዥን የሽረ እንዳስላሰን የመምህራን ሰልፍ አስመልክቶ ያናገራቸው የከተማዋ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የተነሱትን ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ያስተናገደው አንድ ክስተት
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያሰለጠናቸውን እጩ መኮንኖችን ዛሬ ባስመረቀበት መርሐ-ግብር ላይ ተመራቂው ዕጩ መኮንን ተሞሽሯል።
(ምንጭ፡ መከላከያ)
በአሜሪካዋ አላባማ ሁለት ማህፀን ያላት እናት በሁለት ቀናት ውስጥ ሁለት ልጆችን ወለደች።
ከአንድ ሚሊዮን እርግዝና በአንድ እናት ላይ በሚከሰተው በዚህ በሁለት ማህጸን እርግዝና፤ እናት 20 ሰዓታትን በምጥ አሳልፋለች ነው የተባለው።
የ32 ዓመቷ ኬልሲ ሃትቸር ማክሰኞ የመጀመሪያዋን ሴት ልጅ ወለደች፣ ሁለተኛዋን ደግሞ ረቡዕ እለት በአላባማ ዩኒቨርሲቲ በበርሚንግሃም ሆስፒታል በሰላም ተገላግላለች።
እናት ኬልሲ ሃትቸር በማህበራዊ ትስስር ገጿ ላይ ተዓምርኞቹ ስትል የጠራቻቸው ልጀቿ ቤተሰቧን መቀላቀላቸወውን ያታወቀቸወ ሲሆን፤ የህክምና ባለሙያዎችን "አስደናቂ" በማለት አሞካሽታለች።
በሁለቱም ማህጸን ማርገዝ ማለት በቀላሉ ሁለት የተለያየ እርግዝና ተከስቷል እንደማለት ነው የሚሉት የሃቸርን እርግዝና የሚከታተሉት ዶክተር ሪቻርድ ዴቪስ፥ በዚህም ጽንሶቹን መንትያ ማለት እንደሚያስቸግር ይናገራሉ።
በአላባማ ነዋሪ የሆነችው ኬስሊ ሃቸር ከ17 አመቷ ጀምሮ ሁለት ማህጸን እንዳላት የወቀች ሲሆን፤ በአላባማ ዩኒቨርሲቲ በበርሚንግሃም ሆስፒታል እንዲህ አይነት ክስተት 0.3 በመቶ ሴቶች ላይ ሊከሰት እንደሚችል አስታውቋል።
እንደ ሃቸር ሁለት ማህጸን ኖሯቸው ሊፈጠሩ የሚችሉት ከ1 ሺህ ሴቶች ሶስቱ ብቻ ናቸው።
በሁለቱም ማህጸን የመጸነስ እድሉም ከ1 ሚሊየን ሴቶች በአንደኛዋ ይሳካል ተብሎ እንደመታመንም በአላባማ ዩኒቨርሲቲ በበርሚንግሃም ሆስፒታል ገልጿል።
አል አይን
ኢትዮጵያ፦ የእለተ ሀሙስ ኢትዮትዩብ አንኳር አጫጭር ዜናዎች - ታህሳስ 11 ፣ 2016 | #Ethiopia: EthioTube Ankuar : አንኳር - Ethiopian Daily News Digest - December 21 , 2023
👉 ኤርትራ ከአውሮፓ ህብረት ለቀረበባት ወቀሳ ምላሽ ሰጠች
👉 በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት በተባለች ከተማ እና በአቅራቢያዋ ከሰሞኑ ከፍተኛ የሚባል የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተዘገበ
👉 በርካታ የኦነግ ሸኔ አባላት እጅ መስጠታቸው ተነገረ
ሌሎችንም መረጃዎች ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/uXtaj1HlIEg
እስራዔል ኢትዮጵያዊ ዝርያ ያላቸው ዜጎቿን በቴክኖሎጂ ዘርፍ የበለጠ ለማሰማራት የሚያስችል ውጥን ነድፌያለሁ አለች።
የአገሪቱ የሥራ ሚኒስትር እና የስነ ፈጠራ ባለስልጣን በጋራ እንደገለፁት በአገሪቱ የረቂቅ ቴክኖሎጅ (ሃይቴክ) ዘርፍ ውስጥ ቤተ እስራዔላዊያኑ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ መርኃ ግብሮችን በፋይናንስ ለመደገፍ ዕቅድ ተይዟል።
ከፍልስጤማዊው ታጣቂ ቡድን ሐማስ ጋር ጦርነት ውስጥ የምትገኘው እና ከበርካታ ንፁሃን መገደል ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ጫና እየበረታባት ያለችው እስራዔል በቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪ ከሚባሉት ተርታ ትመደባለች። ከአገሪቷ ዓመታዊ አጠቃላይ ምርት ውስጥ እስከ አስራ ስምንት በመቶ የሚሆነው ከዚሁ ዘርፍ እንደሚገኝ ሪፖርቶች ያመላክታሉ። ከቴክኖሎጅ ጋር በተገኘ አዳዲስ ኩባንያዎች ብቅ ከሚሉባቸው አስር አገራት ውስጥ የምትገኘው ቴል አቪቭ ይህም ጥቂት የሕዝብ ቁጥር ይዛ በዝርዝሩ ውስጥ የተገኘች ብቸኛ አገር ያደርጋታል። ከዚህ ጋር ተያይዞም “የአዳዲስ ኩባንያዎች አገር” ወይንም “ስታርታፕ ኔሽን” በሚል ስያሜ ትጠራለች።
ይሁንና የአገሪቱ ዜጋ የሆኑ ቤተ እስራዔላዊያን እና ሌሎችም በአገሪቱ የሚኖሩ ጥቁሮች በቆዳቸው ቀለም ምክንያት መገለል እንዲሁም መዋከብ ይደርስባቸዋል የሚሉ ውንጀላዎች በብዛት ይደመጣሉ።
አሁን ታዲያ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለበትን የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም በዘርፉ የቤተ እስራዔላዊያንን ተሳትፎ ዝቅ ያለ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ሦስት መርኃ ግብሮች ተመርጠው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት አምስት መቶ ሰዎችን ለማሰልጠን ድጋፍ አግኝተዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከወንድ ቤተ እስራዔላዊያን መካከል በቴክኖሎጅ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙት አምስት በመቶ እንኳ አይሞሉም። ከሴት ቤተ እስራላዔላዊያን ደግሞ ይህ ቁጥር 2̄.3 በመቶ ብቻ ነው። ይህን ከቀረው የአገሬው ሕዝብ ዝቅ ያለ ቁጥር ነው ተብሏል።
አደንዛዥ ዕፅ አምርተው ለሽራጭ ሊያቀርቡ የነበሩ አርሶአደሮች ተያዙ።
በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ላዮትርጋ ቀበሌ ውስጥ ተመርቶ ሲዘዋወር የነበረ የአደንዛዥ እፅ ምርት በፖሊስ ሀይል በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።
አደንዛዥ ዕጹ በአርሷ አደር አቶ እንድሪያስ ኢልጎ አማካኝነት ለሽያጭ በከተማ ሲያዘዋውር በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ምርቱን ብቻውን እንዳላመረተና ሌሎች አርሶ አደሮች አብረውት እንዳሉ የእምነት ቃሉን መስጠቱን ተከትሎ ሌሎች 4 አርሶአደሮችም ተይዘዋል።
በዚህም ፖሊስ የፍርድ ቤት ብርበራ ትዕዛዝ በማውጣት በእያንዳንዳቸው የእርሻ ማሳ ተዘርቶ በቅሎ የደረሰው ምርት በመንቀል ዕጹ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታውቋል።
የመጀመሪያ ተጠርጣሪው ዘሩን ከከተማ ማንነቱ ካልታወቀ ግለሰብ ተቀብሎ ማምረት እንደጀመረና ምርቱን ወደ ከተማ በማዘዋወር ላይ እንዳለ በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል።
ኢትዮጵያ፦ የእለተ ረቡዕ ኢትዮትዩብ አንኳር አጫጭር ዜናዎች - ታህሳስ 10 ፣ 2016 | #Ethiopia: EthioTube Ankuar : አንኳር - Ethiopian Daily News Digest - December 20 , 2023
👉 ኢትዮጵያ የአልሸባብ ታጣቂዎች የሽብር ጥቃት ሊያደርሱ ሲሰናዱ ያዝኩ አለች።
👉 ሠራተኞቼ በፀጥታ ኃይሎች ተደብድበዋል ያለው የአፍሪካ የልማት ባንክ የውጭ አገር ባለሞያዎቹን ከኢትዮጵያ ጠቅልሎ ለማስወጣት ወሰነ።
👉 በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ወጥነው የነበሩ የውጭ አገር ኩባንያዎች ፍላጎት ተቀዛቅዟል ተባለ።
ሌሎችንም መረጃዎች ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/eA4UvbXzgdU
ኢትዮጵያ የአልሸባብ ታጣቂዎች የሽብር ጥቃት ሊያደርሱ ሲሰናዱ ያዝኩ አለች።
በቁጥር አስራ አራት ይሆናሉ የተባሉት ታጣቂዎች በምስራቃዊው የሶማሌ ክልል ነበር ጥቃት ሊያደርሱ ያሰቡት ተብሏል። ጥቃቱም ያነጣጠረው የክልሉ መዲና ጅግጅግና ከተማ እና በዙርያዋ ያሉ አካባቢዎች ናቸው ሲል የደህንነት እና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ተናግሯል።
ስለተባለው እስር በዋናነት በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን አልሸባብ ያለው ነገር የለም። አልሸባብ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት በሽብርተኛነት የተፈረጀ ቡድን ሲሆን ለዓመታት ይዞታውን በሶማሊያ ሲያስፋፋ ቆይቷል።
በቅርብ ወራት ግን የሶማሊያ መንግስት በተለያዩ ዙሮች በከፈታቸው ዘመቻዎች የአልሸባብ ይዞታዎችን ለማስለቀቅ ጥረት እያደረገ ነው። የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል አገሪቷን ለቅቆ የሚወጣበት ጊዜ ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ የአገሪቱ ጦር ራሱን ለማጠናከር ብሎም በታጣቂ ቡድኑ ላይ የበላይነትን ለመያዝ እየታተረ ይመስላል።
ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ የተመረጡ የአልሸባብ ዒላማዎች ላይ የድሮን ጥቃቶችን በማድረስ እገዛዋን እያሳየች ነው። አልሸባብ በከተሞች የሽብር ፍንዳታዎች መፈፀሙን መቀጠሉ ግን ይዘገባል። ከጥቂት ወራት በፊት የአልሸባብ ታጣቂዎች ለኢትዮጵያው ሶማሌ ክልል ጠጋ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች ዘመቻዎችን ለማድረግ መሞከራቸው አይዘነጋም።
በሶማሌ ክልል ጥቃት ሊያደርሱ ነበር የተባሉት የአልሸባብ አባላት መሪ አሊ አብዲ በሚል ስም እንደሚጠራ የግብረ ኃይሉ መግለጫ አሳውቋል። መግለጫው አክሎም ይሄው የቡድኑ መሪ በሞያሌ በኩል ሰርጎ ለመግባት ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል ብሏል። ህገ ወጥ የጦር መሣርያዎችን እንዲሁም ሰነዶችንም አብሬ ይዣለሁ ብሏል።
ለሽብር ተግባሩ ሊውሉ የነበር የተባሉት የጦር መሣርያዎቹም በጅግጅግና በዋርዴር እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በተደረጉ እርምጃዎች ተይዘዋል ብሏል።
በሕዳሴው ግድብ ዙርያ ሲደረግ የነበረው ንግግር ያለውጤት ተበተነ።
ግብፅ ኢትዮጵያን ለስምምነት አሻፈረኝ ብላለች በማለት ስትወነጅላት፥ ኢትዮጵያ በበኩሏ ግብፅን የቀኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ተጣብቷታል ስትል ወቅሳታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ ተገናኝተው በግድቡ ዙርያ ተቋርጦ የነበረውን ድርድር ለማስቀጠል እንዲሁም በአፋጣኝ አንዳች ዓይነት ስምምነት ላይ ለመድረስ መወሰናቸውን ከተናገሩ በኋላ ነበር ሦስቱ አገራት ወደጠረጴዛ የተመለሱት። ከዚያም በተለያዩ ጊዜያት በግብፅ መዲና ካይሮ እና በአዲስ አበባ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፤ በዚህ ሳምንትም አራተኛው ዙር ውይይት መጀመሩ ተዘግቦ ነበር። ይሁንና ንግግሩ ያለውጤት መጠናቀቁን ሁለቱ አገራት በየፊናቸው ባወጧቸው መግለጫዎች አሳውቀዋል። በግጭት የምትታመሰው ሱዳን ግን በጉዳዩ ላይ ብዙም ያለችው ነገር የለም።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በቴክኒካዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች ላይ አቋሟን ላላ በማድረግ የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያ አበክራ አሻፈረኝ ብላለች ሲል ውንጀላውን አስደምጧል። በዚህም ሳይወሰን ግብፅ የዓለም አቀፍ ደንቦችን እና ስምምነቶችን በመከተል ውሃዋን እንዲሁም ብሔራዊ ደህንነቷን ከጉዳት የመከላከል መብቷን የሚነካባት የለም ሲል ፈርጠም ብሎ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ ካይሮን በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ላይ ተቸንክራ ስምምነት ላይ እንዳይደረስ እንቅፈት መጋረጥ ይዛለች ሲል ወርፏታል። የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርኆን በመከተል የአሁንም ሆነ የወደፊት ትውልዶች የሚኖሯቸውን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ውሃዋን የመጠቀም መብቷን እውን እንደምታደርግ እጅጉን ግልፅ ማድረግ እንፈልጋለንም ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ።
ግንባታው ስድስት ዓመታትን ይወስዳል ተብሎ አስራ ሁለተኛ ዓመት የደረሰው የህዳሴው ግድብ የውሃ ቋቱ ቢሞላም እና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጭት ቢጀምርም ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ ኤሌክትሪክ የመስጠት ደረጃ ላይ አልደረሰም።
ግብፅ እና ሱዳን ከአባይ ውሃ የምናገኘው ውሃ በግድቡ ምክንያት ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ስሞታን ለዓመታት ሲያሰሙ ቆይተዋል። ግድቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቼ ብርሃን እንዲያገኙ የማደርገው ጥረት አንድ አካል ነው የምትለው ኢትዮጵያ ግን ማንንም የመጉዳት ኃሳብ የለኝም ትላለች።
በየጊዜው በርከት ያሉ ድርድሮች ሲካሄዱ ቢቆዩም አንዳችው ህጋዊ አሳሪነት ያለው ስምምነትን ለማስገኘት አልተቻላቸውም። በበርካታ ጉዳዮች ላይ መግባባት መደረስ መቻሉን ግን ተደራዳሪዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ። ይሁንና በተለይ ድርቅ በሚኖርባቸው ጊዜያት ውሃውን እንዴት ነው የምንጠቀመው እንዲሁም የውሃውን ፍሰት መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው በሚሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ሊደረስ እንዳልቻለ እንዲሁም ጉዳዮቹ አጨቃጫቂ ሆነው መቀጠላቸው ይገለፃል።
በአዲስ አበባ ሲከናወን የቆየው የአሁኑ ንግግር ያለ ፍሬ ከተበተነ በኋላ ቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎችን በተመለከተ የጠራ መረጃ ባይኖርም የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት መግለጫ ድርድሮቹ ዳግም እንደሚቀጥሉ ተስፋ አለኝ ብሏል።
ኢትዮጵያ፦ የእለተ ማክሰኞ ኢትዮትዩብ አንኳር አጫጭር ዜናዎች - ታህሳስ 9 ፣ 2016 | #Ethiopia: EthioTube Ankuar : አንኳር - Ethiopian Daily News Digest - December 19 , 2023
👉 ኢትዮጵያ ያለባት እዳ ሳይከፈል ሌላ ብድር ልትጠይቅ እየተዘጋጀች ነው
👉 ቴዎድሮስ አድሃኖም በአማራ እና በትግራይ ጉዳይ የተናገሩት ምንድነው ?
👉ደቡብ አፍሪካ የቀጣችው ኢትዮጵያዊ ።
ሌሎችንም መረጃዎች ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/lOfbpAosEpk
ታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ/ም ምሽት አዲስ አበባ ቦሌ ኤድና ሞል አካባቢ አንድ ሰው በጥይት ተመቶ ተገድሏል።
ድርጊቱ የተፈፀመው ቦሌ ከኤድናሞል ወረድ ብሎ በሚገኝ አንድ የመዝናኛ ስፍራ አካባቢ ነው።
ምሽት አራት ሰዓት ገደማ ሟች አባተ አበበ በአንድ መሳሪያ በታጠቀ ግለሰብ በጥይት ተመቶ መገደሉ ታውቋል።
አባተ አበበ ተወልዶ ባደገበት ፣ በሚኖርበት አካባቢ እንዲሁም ደግሞ በስራ ህይወቱ በመልካም ስነምግባሩና በተግባቢነቱ በርካቶች እንደሚያውቁት ለመረዳት ችለናል።
ገዳይ እንዳልተያዘ ለመረዳት ተችሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ለሸገር ኤፍ ኤም ሬድዮ በሰጠው ቃል፤ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ ምርመራ ላይ መሆኑን ገልጾ ሲጠናቀቅ በሚዲያ ለህዝቡ ይፋ ይደረጋል ብሏል።
ኢትዮጵያ የጎደለ በጀቷን ለመደጎም ከአይ ኤም ኤፍ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በብድር ለማግኘት እየተጣጣረች ነው።
እስከፈረንጆች 2028 ድረስ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት ያጋጥማታል ተብሏል።
ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር ድርድር ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ክፉኛ የተራቆተ ፋይናንሷም ለማለምለም አይኤምኤፍ ከተለመደው የተለየ የብድር ዕድል እንዲሰጣት ነው ጥያቄ ያቀረበችው።
በጉዳዩ ላይ ዘገባ ያስነበቡ ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች እንደሚሉት ድርድሩ የምጣኔ ኃብቱን መናወጥ በመቀነስ መረጋጋትን መፍጠርን ዓላማ ያደረገ የማሻሻያ መርኃ ግብር ላይ የሚያጠነጥን ነው።
ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ በሚጀመረው የፈረንጆች 2024 የመጀመሪያ ሦስት ወራት ከገንዘብ ተቋሙ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ውጥን ይዛለች።
ከአይኤምኤፍ ከጠየቀችው የ3.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር በተጨማሪ ከዓለም ባንክ ያንኑ የሚያህል የበጀት ድጋፍም ጠይቃለች ኢትዮጵያ።
የውጭ ብድር ጫናቃዋ ላይ ተጭኖ ያጎበጣት እና ግጭቶች ያተራመሷት አገር ከሰሞኑ የብድር ክፍያ አራዝሙልኝ እና የቦንድ ወለድ ቀንሱልኝ ጥያቄዎችን ለተለያዩ አካላት በማቅረብ ተጠምዳለች።
ለቦንድ ገዥዎች የሚጠበቅባትን የ33 ሚሊዮን ዶላር የወለድ ክፍያ ለመፈፀም እንዳልቻለች ባለፈው ሳምንት የተዘገበ ሲሆን በጉዳዩ ላይ አቋሙን የገለፀው የገንዘብ ሚኒስትር የወለድ ክፍያው ያልተፈፀመው መክፈል ስለተሳነን ሳይሆን ሁሉንም አበዳሪዎች በእኩል ደረጃ መመልከት ስለምንፈልግ ነው ማለቱ ይታወሳል። ዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት ግን ከቦንድ ያዥዎች ሰማነው ብለው እንደዘገቡት ኢትዮጵያ በድንገት ነው ክፍያውን መፈፀም እንደማትችል ያሳወቀችው።
ይሄንን ተከትሎም በእፎይታ ጊዜዋ የመጨረሻ ሳምንት ላይ የምትገኝ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ክፍያው የማይፈፀም ካልሆነ ወይንም ደግሞ አንዳች ዓይነት ስምምነት ላይ ለመድረስ ካልተቻለ ዕዳ መክፈል የማይችሉ አገራት ተርታ የመፈረጅ ዕጣ ይገጥማታል። ይህም ዓለም አቀፍ ብድርን ወይንም የፋይናንስ ድጋፍን ለማግኘት እንዲቸግራት ያደርጋል የሚል ስጋት አንዣብቧል።
ከሁለቱ የቻይና አበዳሪ ተቋማት የቻይና ኤግዚም ባንክ እና የቻይና ልማት ባንክ ጋር ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት ለሚቆይ ጊዜ ያህል የብድር ክፍያ ፋታ ለማግኘት ስምምነት ላይ መድረሷ ለምጣኔ ኃብቷ እንደበጎ ነገር ታይቷል። ከአበዳሪዎችም ጋር የ1 ቢሊዮን ዶላር ክፍያ እፎይታን ብታገኝም ይህ እፎይታ ግን ከአይኤምኤፍ ጋር ስምምነት ላይ በመድረሷ ላይ የተንጠለጠለ ነው።
ኢትዮጵያ እንደፈረንጆች ቆጠራ በ2021 ጂ20 እየተባሉ በጅምላ ከሚጠሩት ባለፀጋ አገራት የብድር እፎይታ ጠይቃ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ተፋፍሞ የነበረው ጦርነት እንዲሁም ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ይደመጡ በነበሩ የመብት ጥሰት ውንጀላዎች ምክንያት ንግግሮቹ ምንም ውጤት ላይ ሳይደርስ ቀርቷል።
የጦርነቱ በሰላም ድርድር መቋጨት እንደበጎ እምርታ ቢታይም በሁለት ክልሎች ግጭቶች መቀጠላቸው፥ የሰላም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግም የታየው ዳተኝነት በብድር እፎይታ ጥያቄዎች ላይ ደንቃራ ሆኖ ቆይቷል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአገሪቷ ምጣኔ ኃብት በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም ከከፍተኛ የዋጋ ንረት ወዲያ ወዲህ መላጋት ይዟል። በግጭቶች ምክንያት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መቸገሯም የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ድርቅ አባብሶታል።
ኢትዮጵያ፦ የእለተ ሰኞ ኢትዮትዩብ አንኳር አጫጭር ዜናዎች - ታህሳስ 8 ፣ 2016 | #Ethiopia: EthioTube Ankuar : አንኳር - Ethiopian Daily News Digest - December 18 , 2023
👉 በትግራይ ሽረ እንዳስላሰ መምህራን ከአንድ ዓመት ለሚልቅ ጊዜ ያልከፈላቸውን ውዝፍ ደምወዝ በመጠየቅ አደባባይ ወጡ።
👉 በድርቅ ክፉኛ የተጎዳው የዋግ ኸምራ ዞን አስር ሚሊዮን ብር ገደማ የሚያወጣ ድጋፍ አገኘ፤
👉 በአማራ ክልል የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ 936 ተጠርጣሪዎች ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቀሉ
ሌሎችንም መረጃዎች ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/4ZDQxegfBVM
እስራኤል በጋዛ ድንበር አቅራቢያ ትልቁን የሃማስን ዋሻ ማግኘቷን አስታወቀች
የእስራኤል ጦር በጋዛ ውስጥ ትልቁን የሃማስ ዋሻ ቁልፍ በሆነው የድንበር ማቋረጫ አካባቢ ማግኘቱን ገልጻል።
የእስራኤሉ ባለስልጣናት ዋሻው ከ4 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያለው ሲሆን ከኤሬዝ ድንበር ማቋረጫ በመቶ ሜትሮች ርቀት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። ሃማስ ለጥቅምት 7 ጥቃት ከተጠቀማቸው ዋሻዎች መካከል አንዱ ነው።
የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ በዚህ ዋሻ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር መዋዕለ ንዋይ ፈሷል።
ይህንን መሿለኪያ ለመሥራት ሀማስ ዓመታት ፈጅቶበታል ተሽከርካሪዎች ለማንቀሳቀስ የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል። የእስራኤል ጦር በጋዛ ካደረገው ጦርነት ዋና ዓላማዎች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች የመሬት ውስጥ ዋሻዎችን ማሰናከል እንደሆነም ገልጿል።
በሌላ በኩል የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የእስራኤል የአየር ጥቃት በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ ላይ ቢያንስ 90 ፍልስጤማውያንን ገድሏል። በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው የናስር ሆስፒታል የእናቶች ክፍል ላይ የእስራኤል ጥቃት ቢያንስ አንድ ሕፃን ሲገድል ሌሎች ሦስት ሰዎች ቆስለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሰሜን ጋዛ በሚገኘው በካማል አድዋን ሆስፒታል ላይ የደረሰው ጥቃት አስደንጋጭ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኘውን የሂዝቦላ ፀረ ታንክ ሚሳኤል ማዕከል መትቻለው ስትል ሂዝቦላህ ግን በእስራኤል ወታደሮች ላይ ጉዳት አድርሻለሁ ብሏል። የሶሪያ የሰብአዊ መብት ታዛቢ ቡድን በበኩሉ እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ በፈጸመችው ጥቃት በደማስቆ አቅራቢያ ቢያንስ ሁለት ሰዎችን ገድላለች ብሏል።
በአማራ ክልል የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ 936 ተጠርጣሪዎች ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቀሉ
በሰሜን ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት 936 ተጠርጣሪዎች በሶስት ዙር ምክርና የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባላት በሰሜን ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ለሁለተኛ ዙር በጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ በመጎብኘት ከአመራሩም ጋር ውይይት አድርገዋል።
በጉብኝታቸውም የተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ መልካም መሆኑም ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በሰሜን ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት በአራተኛ ዙር 152 ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።
የሰሜን ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት የዘመቻ ሃላፊ ኮሎኔል መንገሻ ፈንታው እንደገለፁት፤ ኮማንድ ፖስቱ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።
በቀጣናው 779 ተጠርጣሪዎች በሶስት ዙር የተሃድሶ ስልጠና በወስደው እንዲሁም 157 ተጠርጣሪዎች በምክር ወደ ማህበረሰቡ የተቀላቀሉ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በአጠቃላይ 936 ተጠርጣሪዎች በሶስት ዙር የተሃድሶ ስልጠና በምክር ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።
ሊቨርፑል እና ማንችስተር ዩናይትድ ዜሮ ለዜሮ ወተዋል። አርሰናል መሪነቱን ይዟል።
#EPL #PremierLeague
በዚህ ሳምንት በመቀነት መሠናዶ የምዕራፍ አንድ መጠናቀቁን አስመልክተን የነበረንን ቆይታ እናስቃኛቹሀን።
ሙሉውን ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ 👇
https://youtu.be/QSIW570LJbU