† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
[ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል ! ]
" አስማተኛም ፥ መተተኛም ፥ በድግምት የሚጠነቍልም ፥ መናፍስትንም የሚጠራ ፥ ጠንቋይም ፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው ፤ ስለዚህም ርኵሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል።
አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን።" [ ዘዳ.፲፰፥፲፩ ]
🔔
በቤተክርስቲያን የማዕረግ ስም እንደ እንጉዳይ የፈሉ ጠንቋዮች ፣ መተተኞችና አስማተኞች የቤተክርስቲያን መከራዎች ናቸው።
እነዚህ የእግዚአብሔር ተቃዋሚዎችና የዲያብሎስ አገልጋዮች በእጃቸው የብዙ ንጹሐን እንባና ደም አለ። በነዚህ ክፉ ሠራተኞች የተነሳ ብዙ ምስኪኖች በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ይሰቃያሉ። ብዙዎች ሕይወታቸውን ፣ ጤናቸውንና ሰላማቸውን አጥተዋል። ብዙዎችም ሃይማኖታቸውን ክደው ጠፍተዋል። በነሱ ጠንቅ ቤተክርስቲያን ትሰደባለች። ክብረ ክህነት ይደፈራል። ምዕመናን ንጹሕና እውነተኛ የነፍስ እረኞች ካህናትን እንዲጠሉና እንዲርቁ ይሆናሉ። በነዚህ ግለሰቦች የተነሳ ብዙ የዋሃን ገንዘባቸውን ይጭበረበራሉ። ይታለላሉ። ወደ ልዩ ልዩ አጋንንታዊ አሠራሮች ተስበው ይገባሉ።
ስለዚህም በዘመናችን ቤተክርስቲያን በመናፍቃን እንድትሰደብ ፤ ክብረ ክህነትም እንዲደፈር በማድረግ አባቶቻችን ካህናትን ከምዕመናን ለመለየት ሰይጣን ያዘጋጃቸውን እንዲህ ያሉ የዲያብሎስ ሠራዊቶችን ከእኛ ዘንድ እናርቅ ! እንዲህ ያሉት የክፋት ሠራተኞች ለሐሰተኛ አጥማቂያን የገበያ ምንጭ በመሆን እየተመጋገቡ እንደሚሠሩም እናስተውል !
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
🕊
[ † እንኩዋን ለቅዱሳን ጻድቃን "አቡነ መድኃኒነ እግዚእ" : "ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል" እና "ቅዱስ ኪርያቆስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]
🕊 † አቡነ መድኃኒነ እግዚእ † 🕊
መዘንጋታቸው እጅግ ከሚያስቆጭ ኢትዮጽያውያን አባቶች ትልቁን ሥፍራ እኒህ አባት ይወስዳሉ:: የማር ወለላን በሚያስንቅ ጣዕመ ሕይወታቸው ሃገራችንን ያጣፈጡ: ብርሃን ሆነው ብዙ ቅዱሳንን የለኮሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው::
አባ መድኃኒነ እግዚእ የተወለዱት በ፲፫ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ትግራይ [አዲግራት] ውስጥ ነው:: ወላጆቻቸውም ቀሲስ ሰንበትና ሒሩተ ማርያም ይባላሉ:: በደግነትም እጅግ የታወቁ እንደ ነበሩ ገድላቸው ይናገራል:: "መድኃኒነ እግዚእ" ማለት "ጌታ መድኃኒታችን ነው" ማለት ነው::
ብዙ ጊዜም "ዘደብረ በንኮል - ሙራደ ቃል" እየተባሉ ይጠራሉ:: "ደብረ በንኮል" ማለት ትግራይ ውስጥ የሚገኝና ጻድቁ በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ያነጹት ገዳም ነው:: "ሙራደ ቃል" ደግሞ "የቃል [የምሥጢር] መውረጃ" እንደ ማለት ሲሆን በቦታው ሱባኤ የያዘ ሰው ልክ እንደ ቅዱስ ያሬድ ምሥጢር እንደሚገጥለት የሚጠቁም ስም ነው::
ጻድቁ መድኃኒነ እግዚእ በልጅነታቸው ከሊቁ ካህን አባታቸውና ከሌሎችም መምሕራን ተምረው: ምናኔን መርጠው ገዳም ገብተዋል:: በጾም: በጸሎትና በስግደት ተግተው ጸጋ እግዚአብሔር ሲሰጣቸው ወደ ደብረ በንኮል ሒደው ገዳም መሠረቱ::
በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን [በተለይ ከ፲፫ኛው እስከ ፲፭ኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለው] የብርሃን ዘመን ይባላል:: ምክንያቱም ዘመኑ ፦
- ክርስትና ያበበበት::
- መጻሕፍት የተደረሱበት::
- ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት::
- ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው::
ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ :-
- አቡነ ተክለ ሃይማኖት::
- አቡነ ኤዎስጣቴዎስ::
- አባ ሰላማ ካልዕ::
- አቡነ ያዕቆብ::
- ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ::
- አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ::
- አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው::
በተጨማሪም :-
- ፲፪ ቱ ንቡራነ ዕድ::
- ፯ቱ ከዋክብት::
- ፵፯ቱ ከዋክብት::
- ፭ቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር:: ከእነዚህ መካከልም የ፯ቱ እና የ፵፯ቱ ከዋክብት አስተማሪ: የአበው ፫ቱ ሳሙኤሎች [ዘዋልድባ: ዘጣሬጣና ዘቆየጻ] : የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::
ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው: አስተምረው: አመንኩሰው: መርቀው ሰደው: ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ:: ታላቁ ጻድቅና ሰባኬ ወንጌል አባ ዓቢየ እግዚእም [ጐንደር ውስጥ እባብና ጅብ እንዳይጐዳ የገዘቱ አባት ናቸው] የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ነበሩ ይባላል::
ጻድቁ መድኃኒነ እግዚእ በተትረፈረፈ የቅድስና ሕይወታቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: አራዊትን ገዝተዋል: በአንበሳ ጀርባ ላይ እቃ ጭነዋል:: ከረዥም የተጋድሎ ሕይወት በሁዋላም ኅዳር ፫ ቀን ዐርፈዋል:: እድሜአቸውም ፻፹ ነው::
" መድኃኒነ እግዚእ አቡነ መስተጋድል::
ምንኩስናሁ ምዑዝ ከመ ኮል::
በመንፈሰ ጸጋ ክሉል::" [መጽሐፈ ሰዓታት]
" ተአምረ ኃይልከ አባ መድኃኒነ እግዚእ አቡነ::
እም አፈ ዜናዊ ሰማዕነ:: ወበዓይነ ሥጋ ርኢነ::
መንክርኬ አእላፈ ቤትከ ንሕነ::
ባሕቱ በዝ ተአምሪከ ርድአነ::
ለሰይፈ አርዕድ ንጉሥ ዘወሀብኮ ኪዳነ::
ከመ ረድኤቱ ታፍጥን ጊዜ ጸብዕ ኮነ::" [አርኬ]
🕊 † ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል † 🕊
የዚህ ቅዱስ ኢትዮዽያዊ ዜና ሕይወት ለሁላችንም ትልቅ ትምርትነት ያለው ነው:: በተለይ በምክንያት ከቅድስና ሕይወት እንዳንርቅ ያግዘናል ብየም ተስፋ አደርጋለሁ:: የቅዱሱ ወላጆች ገላውዴዎስና ኤልሳቤጥ ሲባሉ በምድረ ሽዋ በበጐ ምጽዋታቸው የተመሰከረላቸው ነበሩ::
ፈጣሪ ሰጥቷቸው ኅዳር ፰ ቀን [በበዓለ አርባዕቱ እንስሳ] ወልደውታልና "ዓምደ ሚካኤል - የሚካኤል ምሰሶ" ሲሉ ሰይመውታል:: ገና በልጅነቱ ብዙዎችን ያስገርም የነበረው ቅዱሱ አንዴ በ ፫ ዓመቱ ከቅዳሴ መልስ ጠፋቸው::
ወላጆቹ እያለቀሱ በሁሉ ቦታ ፈለጉት:: ግን ሊገኝ አልቻለም:: በ3ኛው ቀን የሞቱን መታሠቢያ ሊያደርጉ ካህናትና ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ግን ባዩት ነገር ተገረሙ:: ሕጻኑ ዓምደ ሚካኤል ከቤተ መቅደሱ መሃል: ከታቦቱ በታች ካለው መንበር [ከርሠ ሐመር ይሉታል] ቁጭ ብሎ ይጫወታል::
ያየ ሁሉ "ዕጹብ ዕጹብ" ሲልም አደነቀ:: ምክንያቱም በተፈጥሮ ሥርዓት ሕጻን ልጅ ያለ ምግብ ፫ ቀን መቆየት ስለማይችልና ሕጻኑ በዚያ የቅድስና ሥፍራ ላይ ምንም ሳይጸዳዳ በመገኘቱ ነው::
ብጹዕ ዓምደ ሚካኤል ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየተማረ: በጾምና በጸሎት አደገ:: በ፲፭ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ላይ ንጉሥ የነበረው ጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብም ቅዱሱን የሠራዊት አለቃ [ራስ ቢትወደድ] : ወይም በዘመኑ አገላለጽ የጦር ሚኒስትር አድርጐ ሾመው::
መቼም እዚህ ቦታ ላይ ተቀምጦ መልካምን መሥራት ልዩ ነገርን ይጠይቃል:: በተለይ ደግሞ በዙሪያው የሚከቡትን ተንኮለኞች ድል መንሳቱ ቀላል አልነበረም:: ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ግን በዘመነ ሲመቱ እነዚህን ሠራ:-
፩. በጠዋት ተነስቶ ነዳያንን ይሰበስብና ቁርስ: ምሳ ያበላቸዋል:: ይሕም ዕለት ዕለት የማይቁዋረጥ በመሆኑ ሃብቱ አልቆ ደሃ ሆነ::
፪. ከቀትር በሁዋላ ዘወትር ቆሞ ያስቀድስና ጸበል ተጠምቆ ይጠጣል:: ማታ ብቻ እህልን ይቀምሳል::
፫. ሽፍታ ተነሳ ሲባል ወደ ዱር ወርዶ: ጸልዮ: ሽፍታውን አሳምኖት ይመጣል እንጂ አይጐዳውም::
፬. ጦርነት በሚመጣ ጊዜ ክተት ሠራዊት ብሎ ይወርዳል:: ግን ለምኖ: ጸልዮ: ታርቆ ይመጣል እንጂ ጥይት እንዲተኮስ አይፈቅድም ነበር::
በዚህ መንገድ በ፫ቱ ነገሥታት [በዘርዐ ያዕቆብ: በዕደ ማርያምና እስክንድር] ዘመን ሁሉ አካባቢውን ሰላም አደረገው:: ዓለም ግን ዓመጸኛ ናትና በአፄ እስክንድር ዘመን (በ፲፬፻፸ዎቹ) በሃሰት ተከሶ ስደት ተፈረደበትና ወደ በርሃ ተጋዘ::
በዚያም ቅዱስ ሚካኤል ሰማያዊ መናን እየመገበው: ሥጋ ወደሙን እያቀበለው ኖረ:: ትንሽ ቆይቶ ግን የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በንጉሡ አደባባይ ተገደለ:: ለ፴ ቀናትም በመቃብሩ ላይ የብርሃን ምሰሶ ወረደ በዚህም ንጉሡ በእጅጉ ተጸጸተ::
🕊 † ቅዱስ ኪርያቆስ † 🕊
ሊቅነትን ከገዳማዊ ሕይወት የደረበው ቅዱስ ኪርያቆስ የቆረንቶስ ሰው ሲሆን አበው "ጥዑመ ቃል - አንደበቱ የሚጣፍጥ" ይሉታል:: ገና በልጅነቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያነብ ከአንደበቱ ማማር: ከነገሩ መሥመር የተነሳ ከዻዻሱ እስከ ሕዝቡ ድረስ ተደመው ያደምጡት ነበር::
በወጣትነቱ ጣዕመ ዓለምን ንቆ ከቆረንቶስ ኢየሩሳሌም ገብቷል:: ቀጥሎም ወደ ፍልስጥኤም ተጉዞ የታላቁ አባ ሮማኖስ ደቀ መዝሙር ሁኖ መንኩሷል:: በገዳሙ ለበርካታ ዘመናት ሲኖርም እጅግ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል::
†
💖 [ የትሕርምት ሕይወት ! ] 💖
🕊 💖 🕊
[ በፈተና መጽናትን በተመለከተ ! ]
------------------------------------------------
በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል !
" ተወዳጆች ሆይ በሰው ፊት በአግባቡ ተመላለሱ ፤ በእግዚአብሔርም የበረታችሁ ሁኑ፡፡ እርሱ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና፡፡
ተወዳጆች ሆይ ! ሰዎች ከቤተሰቦቻችሁ ስለምትወርሱት ሀብት ያነሱባችሁ እንደሆነ ፦ “አንተ ሰነፍ ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል ፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል?” ተብሎ ተጽፎአል በሏቸው፡፡ [ሉቃ.፲፪፥፳]
ጨምራችሁም ፦ “ብልሃተኞች እንዲሞቱ ፥ ሰነፎችና ደንቆሮች በአንድነት እንዲጠፉ ፥ ገንዘባቸውንም ለሌሎች እንዲተዉ አይቶአል” ተብሎ ተጽፎአል በሏቸው፡፡ ስለዚህ ገንዘብ መውደድ ለእኔ ጥፋትና የኃጢአት ሥር ነው፡፡
ጌታችንም ፦ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትስብስብ፡፡ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና፡፡” ብሎ አስተምሮኛል በል” ብሎ ይመክራል፡፡ [ማቴ.፮፥፲፱] "
🕊
[ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ]
🕊 💖 🕊
🕊 † 🕊
[ ተዋሕዶ ፍጽምት የቅዱሳን ሃይማኖት ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
[ የሦስቱ ፈቃድ አንድ ነው እንጂ ! ]
🕊
❝ ከሁሉ አስቀድሞ በአካል ልዩ በክብር አንድ የሚሆን ሦስትነትን እናስተምራለን ፥ እሊህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው ፤ ሥላሴ በመለኮት አንድነት መለየት የለባቸውም ፤ አካላት ግን በባሕርይ መለየት ሳይኖር እያንዳንዱ አካል በገጽ ፥ በመልክ ፍጹም ነው።
ለአብ የአባትነት ስም ፤ የአባትነት ክብር አለው ፤ ለወልድም በባሕርይ ክብሩ ከአብ ሳያንስ የልጅነት ስም ፤ የልጅነት ክብር አለው ፤ መንፈስ ቅዱስም እንዲህ በክበር አይለይም ፤ ነገር ግን ተለውጦ አብ ወልድ አይባልም ፤ በዚህ ጊዜ ተገኘ አይባልም ፤ በመለኮት እንደ አብ እንደ ወልድ ነው እንጂ ፤ እስትንፋሳቸው ነውና ሦስቱም ትክክል ናቸውና።
ማንም ማን የጌትነታቸውን ነገር መፈጸም አይችልም ፤ የሦስቱን አካላት ባሕርይ ይለይ ዘንድ ማንም ማን አይድፈር ፤ ሦስቱን አንድ የሚያደርጋቸው ባሕርይ አንድ ነው እንጂ።
ዳግመኛም በየስማቸው በየገጻቸው ሦስቱን አካላት እንወቅ ፤ ከመለኮት ባሕርይ የተለየ አካል የለም ፤ በአካላትም በማይመረመር ክብር መለየት የለም ፤ የሦስቱ ሥልጣን የሦስቱ ፈቃድ አንድ ነው እንጂ። ❞
[ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ]
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፤ ወለወላዲቱ ድንግል ፤ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።
† † †
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 ድምፀ ተዋሕዶ 🕊 ]
🍒▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬🍒
[ ሕይወት የሚገኝባቸው የቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርቶች በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በድምፅ ይቀርባሉ። ]
[ ሳምንታዊ መርሐ-ግብር ]
🕊
❝ የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ፤ ነፍስን ይመልሳል ፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል።
የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው ፥ ልብንም ደስ ያሰኛል ፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው ፥ ዓይንንም ያበራል። ❞
[ መዝ . ፲፱ ፥ ፯ ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
[ ❝ የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ! ❞ ]
[ ክፍል - ፴፫ - ]
💖 ድንቅ ትምህርት 💖
[ በመምህራችን በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ ]
❝ የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል። ❞ [ ምሳ.፩፥፴፫ ]
† † †
▬▬▬▬ ▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬
👇
†
[ 🕊 ክብርት ሰንበት 🕊 ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
❝ ወዮ ይህች ዕለት ያረጀችዋ ያለፈችባት አዲሲቱ የጸናችባት ናት ፤ ወዮ ይህች ዕለት እስረኞች [ ነፍሳት ] የተፈቱባት ባሮች [ ደቂቀ አዳም ] ነጻ የወጡባት ናት። ወዮ ይህች ዕለት የፈረሰ የታነጸባት ሰይጣንም የጠፋባት ናት።
ዳግመኛም ይህች ዕለት በምትሠለጥንበት ጊዜ [ አመ ትሰፍን ወይም ለዘለዓለም ጸንታ በምትኖርበት ጊዜ ] አዲስ ሥራ አዲስ ነገርም ይሆናል ፤ ያን ጊዜ የፀሐይና የጨረቃ የከዋክብትም ብርሃን ፣ ወይም ፀዳል [ ማንም ዓይነት ብርሃን ] ፣ ክረምት ወይም በጋ የለም።
ክብርት የምትሆን ይህች ሰንበተ ክርስቲያን ምን ትደንቅ ! እንደ አብ የሠለጠነች እንደ ወልድ የምትገዛ እንደ መንፈስ ቅዱስ [ ለዘለዓለም ] የምትኖር ናት ፤ ይህች ቅድስት ሰንበተ ክርስቲያን ምን ትደንቅ ! ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምኝልን ፣ ስለኛም አማልጂ ለዘለዓለሙ ! ❞
[ ቅዱስ ያሬድ ]
†
❝ አንተ ግን ከሆድ አውጥተኸኛልና ፥ በእናቴ ጡት ሳለሁም በአንተ ታመንሁ። ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ። ❞
[ መዝ.፳፪፥፱ ]
[ 🕊 ክብርት ሰንበት ! 🕊 ]
† † †
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 ድንግል ሆይ ፦ 🕊 ]
🌼▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬🌼
🌹 ተፈጸመ ናሁ ማሕሌተ ጽጌ 🌹
🕊
❝ ሕብረ ሐመልሚል ቀይሕ ወጸአድዒድ አርአያ ኰሰኰስ ዘብሩር ተአምርኪ ንጹሕ በአምሳለ ወርቅ ግቡር ተፈጸመ ናሁ ማሕሌተ ጽጌ ሥሙር አስምኪ ቦቱ ንግሥተ ሰማያት ወምድር ከመ በሕጽንኪ ያሰምክ ፍቁር ❞
[ የሚያብረቀርቅ ቀይና ነጭ ቀለም ያለው አርአያው የብር ዝንጒርጒር ጠቃጠቆ የኾነ ንጹሕ ተአምርሽ በወርቅ አምሳል የተሠራ ነው ፤ እነሆ የተወደደ [ መልካም ] ማሕሌተ ጽጌ ደረሰ ተፈጸመ ፤ የሰማይና የምድር ንግሥት ማርያም ሆይ የተወደደ ልጅሽ በጒያሽ [ በዕቅፍሽ ] እንዲጠጋ [ እንዲደገፍ ፣ እንዲንተራስ ] በርሱ ዐማጽኚ፡፡ ]
[ አባ ጽጌ ድንግል [ ማህሌተ ጽጌ ] ]
🕊
" ሱላማጢስ ሆይ ተመለሺ ! " [መሓ. ፯:፩]
† † †
💖 🕊 💖
†
🕊 💖 ቅዱስ ማርቆስ 💖 🕊
🕊
❝ አቤቱ የሐዋርያት ተከታዮቻቸው ስለኾኑ ስለ ሰባ ኹለቱ አርድእት ብለኽ በምሕረትኽ ዐስበኝ። ... ስለ እነርሱ ማረኝ ፤ እኔን አገልጋይኽንም በሀገራቸው ውስጥ ከነርሱ ጋር ዕድል ፈንታዬን ጽዋ ተርታዬን አድርግ ፤ አሜን። ❞
[ ተአምኆ ቅዱሳን ]
▬▬▬▬▬▬ ♱ ▬▬▬▬▬▬
[ ከማርቆስ ወንጌል ]
❝ ወደ ተራራም ወጣ ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ ❞ [ ማር . ፫ ፥ ፲፫ ]
🕊
[ † እንኳን ከ፸፪ [ 72 ] ቱ አርድእት አንዱ የሆነ: ወንጌላዊ: ሐዋርያ: ሰማዕት: ዘአንበሳና ርዕሰ ሊቃነ ዻዻሳት የተባለ ቅዱስ ማርቆስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]
🕊 💖 🕊
🕊 💖 ▬▬ † ▬▬ 💖 🕊
[ 🕊 መዝሙረ ተዋሕዶ 🕊 ]
[ ኦርቶዶክሳዊ የተቀደሰ ያሬዳዊ ዝማሬ ሰዓት ]
[ ሳምንታዊ መርሐ-ግብር ]
🕊
በስመ አብ ፡ ወወልድ ፡ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ንጹሕና የተቀደሰ ነው ፥ ለእግዚአብሔር ምስጋናና ልመና የሚቀርብበት ፣ ይቅርታና ምሕረት የሚጠየቅበት ፣ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት የሚዘጋጅ ንጹሕ መስዋዕት ነው ፥ በአበው ጸሎት ይዘጋጃል ፥ ከስጋዊና ከደማዊ ሀሳብ የራቀ ነው ፥ ልቦናን ወደ ንስሐ ይጠራል ፥ ከኃጢአትና ከክፉ ሥራ የመለየት ኃይል አለው ፥ ክፉ መንፈስን ከሰው ልብ ያርቃል ፥ መረጋጋትን ልቦናን ዘልቆ የሚሰማ ውስጣዊ ሰላምን ይሰጣል ፥ በአሚነ ሥላሴ ያጸናል ፥ የክርስቶስን የባህርይ አምላክነትና መሐሪነት ይመሰክራል ፥ የእመቤታችንን ፍቅር በልቦና ያሳድራል ፥ በእናትነቷና በምልጃዋ እንድንታመን ያደርጋል ፥ በቅዱሳን ጸሎትና በቃል ኪዳናቸው ያጸናናል ፥ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እናውቅ ዘንድ መንገድ ይመራናል ፥ ፈሪሐ እግዚአብሔርንና ፍቅረ እግዚአብሔርን ያጎናጽፈናል፡፡
▬▬▬▬▬▬ ♱ ▬▬▬▬▬▬
ተወዳጆችሆይ ፦ በተቀደሰ ሰማያዊ ያሬዳዊ ዜማ ነብሳችንን እናስጊጣት፡፡ ከደጋጎቹ አባቶቻችን ጋር ከዓለም ርኩሰት በተለየ የተቀደሰ ዝማሬ አምላካችን እግዚአብሔርን እናመሥግን፡፡ ለስጋዊ ጆሮዎች ከሚመች ከረከሰ የተሃድሶ የኑፋቄ እርሾ ልቦናችንን እንጠብቅ፡፡ ገንዘብን ስለመውደድ ከሆነ ከሥጋዊ ሥራ ፈጽሞ እንለይ፡፡
🍒
❝ እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።
በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና ፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና ፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና። ❞
{ መዝ . ፳፯ ፥ ፬ }
† † †
💖 🕊 💖
🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †
† ጥቅምት ፴ [ 30 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †
🕊 † ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ † 🕊
በዚሕች ዕለት ከ፸፪ ቱ አርድእት አንዱ የሆነ: ወንጌላዊ: ሐዋርያ: ሰማዕት: ዘአንበሳና ርዕሰ ሊቃነ ዻዻሳት የተባለ ቅዱስ ማርቆስ ተወልዷል ::
ቅዱስ ማርቆስ እናቱ ማርያም: አባቱ አርስጥቦሎስ ይባላሉ:: በልጅነቱ ኦሪትንና የዘመኑን ጥበብ ሥጋዊ በሚገባ ተምሮ ክርስቶስን ከቤተሰቦቹ ጋር ተከትሏል:: የመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን ከ፻፳ው ቤተሰብ በእድሜ በጣም ትንሹ /፳ ዓመት/ እርሱ ነበር::
ለ፫ ዓመታት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ ደክሟል:: በተለይ የግብፅና የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው:: ክህነትን ያገኘን ከርሱ ነውና::
ቅዱስ ማርቆስ ፲፮ ምዕራፍ ያለውን ወንጌሉን ሲጽፍ ኪሩብ ገጸ አንበሳ በቀኙ: ሊቀ ሐዋርያት በግራው ሆነው ይራዱት ነበር:: ቅዱሱ ክቅዱስ ዻውሎስ: ከበርናባስና ዼጥሮስ ጋር ተጉዟል:: ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ሰሜን አፍሪካ አካባቢ አረማውያን ገድለውታል:: ይህቺ ዕለት የልደቱ መታሠቢያ ናት::
ዳግመኛ በዚህ ቀን የቅዱስ ማርቆስን ወላጆችን እናስባቸው ዘንድ ይገባል:: ቅዱስ አርስጥቦሎስ [አባቱ] የጌታ ቅን አገልጋይ የነበረ: ቅድስት ማርያም [እናቱ] ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ: ጌታችንን ያገለገለች ቤቷን ለሐዋርያትና ለጌታ በስጦታ ያበረከተች ቅድስት ናት::
ቤቷም [ጽርሐ ጽዮን] የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ይህች ቤት መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል:: የእመቤታችን ግንዘትም ተከናውኖባታል::
እግዚአብሔር ከሐዋርያዊው ቅዱስ ቤተሰብ በረከትን ያድለን::
🕊 † ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ † 🕊
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: [ሉቃ.፩፥፮]
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ [አድናቆት] ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ፺ የዘካርያስ ፻ ደግሞ ደርሶ ነበር::
ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት [ኢሳ.፵፥፫, ሚል.፫፥፩] ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ፮ ወራት ራሷን ሠወረች:: በ፮ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ [ሰገደ]:: ከዚህ በኋላ በዚህች ቀን [ሰኔ ፴] ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::
ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ፪ ዓመት ከ፮ ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::
እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ፫ [፭] ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ ፭ [፯] ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት::
ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::
ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ፳፭ [፳፫] ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::
ከዚህ በኋላ ፴ ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: [ኢሳ.፵፥፫, ሚል.፫፥፩] አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" [ሉቃ.፩፥፸፮] ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::
ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::
ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ፮ ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::
"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ፯ ቀናት አሠረው::
በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: [ማቴ.፫፥፩, ማር.፮፥፲፬, ሉቃ.፫፥፩, ዮሐ.፩፥፮]
ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::
†
💖 [ የትሕርምት ሕይወት ! ] 💖
🕊 💖 🕊
[ በፈተና መጽናትን በተመለከተ ! ]
አጋንንት እንደ ነጣቂ ተኩላዎች ናቸው !
" ሰዎች ከዚህ ዓለም አስተሳሰብ ወጥተው ስለ ሰማያዊው ሕይወታቸው መጨነቅ ሲጀምሩ ለመንፈሳዊው ሕይወት የምናደርገውን ተጋድሎ አጋንንት መቋቋም ሲያቅታቸው የሰውን አእምሮ በልዩ ልዩ ሐሳቦች እንዲረበሽ በማድረግ ሰውን ከመንፈሳዊው ተጠምዶው ለማውጣት አቅደው ይንቀሳቀሳሉ፡፡
ለዚህ የተዘጋጀ በእምነቱ ያልጠነከረ እና ተጠራጣሪ ሰው ካገኙ ግን ከመንገዱ ያስቱታል፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ የመጣብንን ፈተና በጽናት ከታገልን እግዚአብሔር አምላክ እነርሱን ከእኛ አስወጥቶ ይሰዳቸዋል፡፡ እኛም እንደ አዲስ የወይን ጠጅ ሆነን በመንፈስ ቅዱስ ጣፍጠን እንገኛለን፡፡
አጋንንት እንደ ነጣቂ ተኩላዎች ናቸው፡፡ እነርሱ በትሕርምት ሕይወት ወደሚኖረው ተሐራሚ በአት ለመግባት ትንሽ ቀዳዳ እስከሚያገኙ ድረስ ያደባሉ፡፡ መግቢያ ቀዳዳን ሲያገኙ ፈጥነው በመግባትና አእምሮን በመለወጥ ነፍስን ወደ ጥፋት ይመሯታል፡፡
በዚህ ፈተና ውስጥ ያለ ተሐራሚ ግን አጋንንት ወደ እርሱ ይገቡ ዘንድ አንዳች ክፍተት ካልተወ ተስፋ በመቁረጥ ከእርሱ ይርቃሉ፡፡ ስለዚህ የአጋንንትን ውጊያ በመፍራት ከጽድቅ ሕይወት አትውጡ ፣ በኃጢአት ያሳድፉኛል ብላችሁም አትስጉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተን ይረዳችኋል ምንም ሊጎዷችሁ አይቻለውም፡፡
እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ ፦ “ እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና፡፡” [፪ጢሞ.፩፥፯] ጌታችንም ለሐዋርያት ፦ “ ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም፡፡ [ሉቃ.፲፥፲፰] በማለት ከእንግዲህ በእኛ ላይ ስልጣን እንደሌላቸው አስተምሮናል፡፡ "
[ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ]
🕊 💖 🕊
🕊 † 🕊
[ ተዋሕዶ ፍጽምት የቅዱሳን ሃይማኖት ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
[ እምነታችንም በዕሩቅ ብእሲ አይደለም ! ]
🕊
❝ ድኅነታችንም በዕሩቅ ብእሲ አይደለም ፥ እምነታችንም በዕሩቅ ብእሲ አይደለም ፥ መጽሐፍ በዕሩቅ ብእሲ የሚያምን ርጕም ይሁን ብሏልና" [ዘዳግ.፳፯፥፲፭]
ክርስቶስ ዕሩቅ ብእሲ እንደሆነ ስለሚናገሩ ሰዎች ምን እንላለን ? እርሱ እግዚአብሔር ቃል እንደሆነ በሁሉ ዘንድ የታወቀ የተረዳ ሲሆን ፥ እኛ ግን እግዚአብሔር ቃል ሰው እንደ ሆነ ያለመጠራጠር እናምንበታለን ፥ በእውነት ሰው ኾነ እንጂ በሐሰት አይደለም።
ዕሩቅ ብእሲ ሆኖ ከዚህ በኋላ መለኮት ያደረበት አይደለም ፥ አለኝታችን ደኅንነታችን ከዕሩቅ ብእሲ የተገኘ አይደለም።
ከአዳም ጀምሮ እስከ ዛሬ ከተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ማንም ማን ሊያድነን አልቻለም ፤ ከእግዚአብሔር ቃል በቀር ፥ በሰው ቢሆን አለኝታችን ከንቱ እንዳይሆን የባሕርይ አምላክ እርሱ ሰው ኾነ እንጂ። ❞
[ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ]
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፤ ወለወላዲቱ ድንግል ፤ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።
† † †
💖 🕊 💖
🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †
[ እንኩዋን ለአበው ቅዱሳን "ሳሙኤል ዘወገግ": "ጸቃውዐ ድንግል" እና "ድሜጥሮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ። ]
🕊 † አባ ሳሙኤል ዘወገግ † 🕊
ሃገራችን ኢትዮዽያ ማኅደረ ቅዱሳን [ምዕራፈ ቅዱሳን] እንደ መሆኗ ፍሬ ክብር: ፍሬ ትሩፋት ያፈሩ ብዙ አባቶችና እናቶችን አፍርታለች:: ብርሃን ሁነው ካበሩላት ቅዱሳን መካከል አንዱ ደግሞ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ ናቸው::
በእኛው ሃገር ብቻ ብዙ "ሳሙኤል" የሚባሉ ቅዱሳን በመኖራቸው ስንጠራቸው "ዘእንትን" እያልን ነው:: ለምሳሌም:
- ሳሙኤል ዘዋሊ
- ሳሙኤል ዘወገግ [የዛሬው]
- ሳሙኤል ዘጣሬጣ
- ሳሙኤል ዘቆየጻ
- ሳሙኤል ዘሃሌ ሉያና
- ሳሙኤል ዘግሺን መጥቀስ እንችላለን:: ሁሉም የመካከለኛው ዘመን ሐዋርያዊ አባቶች ናቸው::
ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ የተወለዱት በ፲፫ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው የብዙ ቅዱሳን ቤት የሆነችው ሽዋ ናት:: መንደራቸውም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ብዙም አይርቅም::
የጻድቁ ወላጆች እንድርያስና አርሶንያ የሚባሉ ሲሆን ደጐች ነበሩ:: ጻድቁ በተወለደ ጊዜ የቤታቸው ምሰሶ ለምልሞ ተገኝቷል:: አቡነ ሳሙኤል ከልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው በጉብዝናቸው ወራት ይህችን ዓለም ንቀዋል::
የታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው በደብረ ሊባኖስ መንነዋል:: ከ፲፪ቱ ኅሩያን [ምርጦች] አርድእት አንዱ ነበሩና በክህነታቸው ደብረ ሊባኖስን ተግተው ያጥኑ ነበር:: በዚያውም በንጹሕ ልቡና በጾምና ጸሎት ይተጉ ነበር::
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በሁዋላ በደጉ ዻዻስ በአቡነ ያዕቆብ ዘመን ፲፪ቱ ንቡራነ እድ ተመረጡ:: እነዚህ አባቶች በወንጌል አገልግሎት: በተለይ ደቡብና ምሥራቁን የሃገራችን ክፍል ያበሩ ናቸው:: ቅዱሳኑ ሲመረጡም ከአቡነ ፊልዾስ ቀጥለው በ፪ኛ ደረጃ የተመረጡ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ ናቸው::
ሃገረ ስብከታቸውም ሐረርና ሱማሌ ነበር:: ጻድቁ በሃገረ ስብከታቸው ወርደው በሐረርና ሱማሌ አካባቢ ለዘመናት የወንጌልን ዘር ዘርተው እልፍ ፍሬን አፍርተዋል:: አካባቢውንም መካነ ቅዱሳን አድርገውታል::
ቀጥለው ገዳማዊ ሕይወትን ያጸኑ ዘንድ በምሥራቁ የሃገራችን ክፍል በአፋር ሱባኤ ገቡ:: ቦታውም ደብር ሐዘሎ ነበር:: በቦታው ለ፻፶፭ ቀናት ከቆሙ ሳያርፉ: ከዘረጉ ሳያጥፉ: እህል ውሃ ሳይቀምሱ ጸለዩ::
በሱባኤያቸው ፍጻሜ ግን ቅዱስ መልአክ መጥቶ "ሳሙኤል ወደዚያ ተራራ ሒድ:: የስምህ መጠሪያ እርሱ ነውና:: ይህ ግን የሌላ ሰው [የአባ አንበስ ዘሐዘሎ] ርስት ነው" አላቸው:: ጻድቁም ወዳላቸው ተራራ ሒደው ቢጸልዩ ከሰማይ ብርሃን ወረደላቸው::
በመንፈቀ ሌሊት የበራው ብርሃን እስከ ጐረቤት መንደር ሁሉ በመድረሱ የአካባቢው ሰው "ወገግ አለኮ-ነጋ" ብለውዋል:: በዚህ ምክንያት ዛሬም "ደብረ ወገግ" ይባላል:: ይህ ቦታ ዛሬም ድረስ ንጹሕ ልብ ላላቸው አበው በብርሃን ተከቦ ይታያል::
ጻድቁ የወለዷቸው ብዙ ሥውራንም በሥፍራው ይገኛሉ:: ቦታው የአንበሶች መኖሪያ በመሆኑ ጠላት መናንያኑን ማጥቃት አይችልም:: ሳሙኤል ዘወገግም የሚጸልዩት በአናብስት ተከበው ነበር:: በቦታው አንዳንዴም አንበሶች ሲሰግዱ ይታያል ይባላል:: ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ግን እንዲህ በቅድስና ተመላልሰው በ፲፬ኛው መቶ ክ/ዘመን ሱማሌ ክልል ውስጥ በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: የጻድቁ ልደት ሐምሌ ፱ : ፍልሠታቸው ደግሞ ግንቦት ፳፯ ነው::
🕊 † አባ ጸቃውዐ ድንግል † 🕊
እኒህ ጻድቅም ኢትዮዽያዊ ናቸው:: የስማቸው ትርጉም "የድንግል ማርያም ወለላ ማር" ማለት ሲሆን ዜና ሕይወታቸው እንደ ስማቸው ጣፋጭ ነው::
የእኒህ ጻድቅ አባታቸው የተመሰከረላቸው ሊቅና የገዳም መምሕር ናቸው:: ምክንያቱም ጸቃውዐ ድንግልን ከወለዱ በሁዋላ መንነዋልና:: አባት የደብረ ዘኸኝ መምሕር ሳሉ ልጃቸው ጸቃውዓ ድንግልን ወደ ገዳሙ ወስደው አሳደጉዋቸው::
በዚያውም ጾምና ጸሎትን: ትዕግስትና ትሕርምትን አስተማሯቸው:: ቅዱሳት መጻሕፍትንም በወጉ አስጠኗቸው:: አባ ጸቃውዐ ድንከግልም በጐውን የምናኔ ጐዳና ከተማሩ በሁዋላ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበሉ::
፵ ዓመት ሲሞላቸው ግን አባታቸው ዐረፉ:: መነኮሳት አበውም ተሰብስበው "ከአንተ የተሻለ የለም" ሲሉ ጸቃውዐ ድንግልን የደብረ ዘኸኝ መምሕር አድርገው ሾሟቸው:: ጻድቁም ቀን ቀን ሲያስተምሩ ይውሉና ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ ያድሩ ነበር::
በሌሊትም ከባሕሩ ወጥተው የአካላቸው ርጥበት ደርቆ ላበታቸው እስኪንጠፈጠፍ ድረስ ይሰግዱ ነበር:: በዚህ መንገድም ራሳቸውን ገዝተው: መነኮሳትንም ገርተው ያዙ:: እግዚአብሔርም ክብራቸውን ይገልጽ ዘንድ ብዙ ተአምራትን በእጃቸው አሳይቷል::
አንድ ቀን አባ ጸቃውዐ ድንግል መንገድ ሲሔዱ ሁለመናው በቁስል የተመታ አንድ መጻጉዕ ነዳይ ወድቆ አዩ:: ወደ እርሱ ሲደርሱ ምጽዋትን ለመናቸው:: ጻድቁ ግን "የምሰጥህ ነገር የለኝም:: ግን የፈጣሪየን ስጦታ እሰጥሃለሁ" ብለው: በውሃ ላይ ጸልየው ረጩት::
ያ መጻጉዕም አካሉ ታድሶ: እንደ እንቦሳ ዘሎ ተነሳ:: ደስ እያለው: ፈጣሪውንም እያከበረ ወደ ቤቱ ሔዷል:: አባ ጸቃውዐ ድንግልም በዚህች ቀን ዐርፈው በገዳማቸው ተቀብረዋል::
🕊 † ቅዱስ ድሜጥሮስ ሰማዕት † 🕊
ይህ ቅዱስ በዘመነ ሰማዕታት: በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከነበሩ ክርስቲያኖች አንዱ ነው:: ቅዱስ ድሜጥሮስ ስቅጣር ከሚባል ደግ ባልንጀራው ጋር በበጐው ጐዳና ሲኖሩ የመከራው ዘመን ደረሰ:: መወሰን ነበረባቸውና ፈጣሪያቸውን ከሚክዱ ሞትን መረጡ::
አስቀድሞም ሲያስተምር በመገኘቱ ቅዱስ ድሜጥሮስ በንጉሡ እጅ ወደቀ:: ንጉሡ መክስምያኖስም እሥራትን አዘዘበት:: በዚያ ወራት ደግሞ የንጉሡ ወታደር የሆነና በጣዖት የሚመካ አንድ ጉልበተኛ ነበር::
ማንም በትግል አሸንፎት ስለማያውቅ ጣዖታዊው ንጉሥ ይመካበት ነበር:: አንድ ቀን ግን አንድ ክርስቲያን ወደ እሥር ቤት ገብቶ ቅዱስ ድሜጥሮስን "ባርከኝና ያንን ጣዖታዊ ጉልበተኛ እጥለዋለሁ" አለው::
የቅዱሱን ጸሎትና በረከት ተቀብሎም በንጉሡ አደባባይ ታግሎ ጣለው:: ንጉሡና የጣዖቱ ካህናትም በእጅጉ አፈሩ:: በሁዋላ ግን ይህንን ያደረገው ቅዱስ ድሜጥሮስ መሆኑ በመታወቁ ከባልንጀራው ቅዱስ ስቅጣር ጋር በዚህች ቀን ገድለዋቸዋል::
አምላከ አበው ቅዱሳን ጸጋ ክብራቸውን ያብዛልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
🕊
[ † ጥቅምት ፳፱ [ 29 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. አቡነ ሳሙኤል ጻድቅ [ዘደብረ ወገግ]
፪. አባ ጸቃውዐ ድንግል [ዘደብረ ዘኸኝ]
፫. ቅዱስ ድሜጥሮስ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ስቅጣር ሰማዕት
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. የፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
፪. ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፬. ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
፭. ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ
፮. ቅድስት አርሴማ ድንግል
†
💖 [ የትሕርምት ሕይወት ! ] 💖
🕊 💖 🕊
[ በፈተና መጽናትን በተመለከተ ! ]
አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል !
❝ ክፉ ሐሳብም ወደአእምሮህ በገባ ጊዜ በልቅሶ ሆነህ ፦ “ጌታዬ ሆይ ራራልኝ ኃጢአተኛ ነኝና ይቅር በለኝ ሰውን ወዳጅ ሆይ ይህ ክፉ ሐሳብ ከእኔ አውጥተህ ጣልልኝ” ብለህ ወደ አምላክ በነፍስህ ጩኽ፡፡
እግዚአብሔር በሕሊናህ የሚመላለሰውን ሐሳብ ያውቃልና እርሱ ከክፉ ፈቃድ የሆነውን አስተሳሰብ ይለያልና፡፡ እንዲሁ ከሚዋጉን ክፉ አጋንንት እንጂ ከእኛ ያልመነጨውን የእኛ ሐሳብ አስመስለው በአእምሮአችን ያስገቡትን የአጋንንትን ሥራ ያውቃል፡፡
ይህንን ልብ በል ፤ ብዙ በተጋደልህና በጽናት ሆነህ ጌታህን ባገለገልኽ ቍጥር አእምሮህና አስተሳሰብህ የፊትን መልክ እንደሚያሳይ ጥርት እንዳለ ውኃ ከክፉ ሐሳብ ንጹሕ ይሆንልሃል፡፡ ይህም ጌታችን “...ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል” ብሎ እንደተናገረው ነው፡፡ [ዮሐ.፲፭፥፪]
ምክንያቱም ጌታችን ከእኛ የሚሻው እና እርሱ ሊያግዘን የሚወድደው መዳናችንን ለመፈጸም በጽናት ሆነን የተጋደልን እንደሆነ ብቻ ነውና፡፡ ክፉ አስተሳሰቦችን በተመለከተ ጌታችን የተናገረውን ልብ በሉ ፦ ወይኑ በተገረዘ ጊዜ ፍሬው ወይን ጠጅ ይሰጥ ዘንድ በመጥመቂያው ውስጥ ይጣላል ፣ በእግርም ይረገጣል ፣ ከዚያም ወይን ጠጅ ለመሆን ይዘጋጃል፡፡ የተረገጠው ወይን የወይን ጠጅ ለመሆን እንዲፈላ ይደረጋል፡፡ ወይኑ ከመፍላቱ የተነሣ የሚፈላበት ጋን የወይኑን ኃይል መቋቋም ስለማይችል ጋኑን እንዳይሠብረው ሲባል መግጠሚያው ይነሣል፡፡ እንዲሁ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ይህ ይሆናል፡፡ ❞
[ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ]
🕊 💖 🕊
💛
🕊 ቅ ዱ ስ አ ማ ኑ ኤ ል 🕊
❝ ሰላም ለአስተርእዮቱ በሥጋ
ዘአስተርአየ ገሃድ ከመ የሀበነ ጸጋ ❞
[ በግልጽ ጸጋን ያድለን ዘንድ በሥጋ የተገለጠ ለኾነ ለእርሱ አገላለጥ ሰላምታ ይገባል ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
❝ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል ፤ እነሆ ፥ ድንግል ትፀንሳለች ፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች ፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ❞
[ ኢሳ.፯፥፲፬ ]
" Therefore the Lord himself shall give you a sign; Behold, a virgin shall conceive, and bear a son, and shall call his name Immanuel."
[ Isaiah 7:14 ]
🕊 💖 🕊
👇
በ፫፻፹፩ ዓ/ም መቅዶንዮስ: አቡሊናርዮስና ሰባልዮስ በካዱ ጊዜም ለጉባኤው ወደ ቁስጥንጥንያ ከሔዱ ሊቃውንት አንዱ ይሔው ቅዱስ ኪርያቆስ ነው:: ወደ ጉባኤው የሔዱትም ከታላቁ ሊቅና የኢየሩሳሌም ሊቀ ዻዻሳት ቅዱስ ቄርሎስ መንፈሳዊ ጋር ነው::+ሁለቱ እጅግ ወዳጆች ነበሩና:: በጉባኤውም መናፍቃንን ረትተው: ሃይማኖትን አጽንተው: ሥርዓትን ሠርተው ተመልሰዋል:: ቅዱስ ኪርያቆስም በተረፈ ዘመኑ በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል:: አምላከ አበው የወዳጆቹን የቅድስና ምሥጢር ለእኛም ይግለጽልን:: በረከታቸውንም አትረፍርፎ ይስጠን::
[ ኅዳር ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ጻድቅ [ዘደብረ በንኮል]
፪. ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ጻድቅ [የሠራዊት አለቃ]
፫. ቅዱስ ኪርያቆስ ሊቅ
፬. ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ንጉሥ [ልደቱ]
፭. ቅዱሳን አትናቴዎስና እህቱ ኢራኢ [ሰማዕታት]
፮. አቡነ ፍሬ ካህን
[ ወርኀዊ በዓላት ]
፩. በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው [ዘካርያስና ስምዖን]
፬. አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭. አቡነ ዜና ማርቆስ
፮. ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ [ዓምደ ሃይማኖት]
"በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል::" [ምሳሌ.፲፥፮]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
†
❝ አጽናኑ ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ❞ [ ኢሳ.፵፥፩ ]
❝ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ ፤ በርታ ፥ ልብህም ይጽና ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ። ❞ [ መዝ.፳፯ ፥ ፲፬ ]
በሌላ ስፍራም ፦
❝ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ ፤ አበረታሃለሁ ፥ እረዳህማለሁ። ❞ [ ኢሳ.፵፩ ፥፲ ]
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 ገ ድ ለ ቅ ዱ ሳ ን 🕊 ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
[ የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ የተጋድሎ ሕይወቱና ትምህርቱ ]
[ ክፍል ሠላሳ አምስት ]
💛
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
[ የአጋዘን ግልገሎችን እንደ ፈወሰ ! ]
🕊
❝ አባ መቃርዮስ እንዲህ አለ ፡- “ አንድ ወቅት በበረሓው የሰሌን ቅርንጫፍ እየሰበሰብኩ ሳለ አንዲት አጋዘን ወደ እኔ መጣችና ፀጉሯን እየነጨች ዕንባዋ ወደ መሬት እስኪወርድ ድረስ ታለቅሳለች፡፡ ራሷን መሬት ላይ ጥላ ከእግሬ ጫፍ ላይ ወድቃ በዕንባዋ እግሬን አራሰችው፡፡ እኔም በዕንባዋ መፍሰስና በሁኔታዋ ተገርሜ ቁጭ አልኩና ፊቷን ዳስሼ በእጆቼ ቀባኋት ፣ እርሷም ትኩር ብላ ታየኝ ነበር፡፡ ከዚያም አጽፌን ያዘችና ትጎትተኝ ጀመር፡፡ እኔም ተከተልኳት፡፡
“ወደ ምትኖርበት በወሰደችኝ ጊዜ በዚያ ሦስት ልጆቿ ተኝተው አገኘሁ፡፡ ቁጭ ባልሁ ጊዜ እነዚያን ልጆቿን በየተራ እያመጣች ጭኔ ላይ አደረገቻቸው፡፡ በነካኋቸው ጊዜም አካላቸው የተበላሸና ችግር ያለበት መሆኑን ተረዳሁ ፣ ፊታቸው ወደ ኋላቸው የዞረ ነበር፡፡ እናታቸው እያለቀሰች ነበር ፡ እኔም አሳዘኑኝና እንዲህ እያልሁ ስለ እነርሱ ወደ አምላኬ ጮኽኩ ፡-
'እጅግ ብዙ የሆነ የምሕረት መዝገብ ያለህና ለፍጥረቱ ሁሉ የምታስብ አምላክ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እባክህ በፈጠርካቸው ፍጥረታትህ ላይ ምሕረትህን አድርግላቸው ፤ እዘንላቸው፡፡ በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እነዚህን ቃላት በዕንባ ሆኜ በተናገርኩ ጊዜ እጆቼን ዘርግቼ በአጋዘኗ ልጆች ላይ አዳኝ የሆነ የመስቀልን ምልክት አደረግሁ [ አማተብሁ ] ፣ ያን ጊዜም ተፈወሱ፡፡ ከጭኔ ባወረድኳቸው ጊዜ እናታቸው ወዲያውኑ ተቀበለቻቸውና ትንከባከባቸው ጀመረች፡፡
እነርሱም ወደ ጡቶቿ ሄደው ይጠቡ ጀመር፡፡ እርሷም በእነርሱ መፈወስ እጅግ በጣም ደስ አላት፣ በታላቅ ደስታ ሆና ዓይን ዓይኔን ትክ ብላ ትመለከተኛለች፡፡ እኔም ለእኔ ባደረገው ቸርነትና ለሚያስብላቸው ለሌሎች እንስሳትም ባለው መጋቢነት እግዚአብሔርን አደነቅሁ፡፡ እግዚአብሔርን ስለ ደግነቱና ቸርነቱ ፣ ለእያንዳንዱ ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ስላለው የቸርነት ብዛት እያመሰገንሁ ተነሥቼ ሄድኩ፡፡ ❞
የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃና ጸሎቱ አይለየን፡፡
ይቆየን !
† † †
💖 🕊 💖
🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። †
✞ ኅዳር ፪ [ 2 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞
🕊 † አባ ዼጥሮስ ሣልስ † 🕊
✞ 'ዻዻስ' ማለት 'አባት-መሪ-እረኛ' ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ ፫ ናቸው:: እነሱም ዲቁና: ቅስና: ዽዽስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ ፱ ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ዽዽስና ነው::
ዽዽስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር 'ሸክም: ዕዳ' ሲሆን በሰማይ ግን 'ክብር' ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ዽዽስናን አይመኝም::
ቅዱስ ዻውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ-ማንም ዽዽስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" [፩ጢሞ.፫፥፩] ማለቱን ይዞ 'ሹሙኝ' ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የዻዻሱ ነው::
አንድ ዻዻስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ-መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" [ዮሐ.፲] ስለዚህም ክህነት / ዽዽስና ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው::
አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የዽዽስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ዽዽስናዎች ፬ቱ የበላይ ናቸው:: እነዚህም የቅዱስ ዼጥሮሱ የሮም: የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ: የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ዻውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው::
እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ ፬፻፵፫ [፬፻፶፩ ዓ/ም : ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው [የግብጹ] እና የአንጾኪያው [የሶርያው] ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው::
የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ዻዻሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች::
በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን:: እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና:: ከእነዚህም መካከል አንዱ አባ ዼጥሮስ ሣልሳዊ ነው::
ሣልሳዊ መባሉ ከእርሱ በፊት በዚህ ስም ተጠርተው በመንበረ ማርቆስ ላይ የተቀመጡ 2 ፓትርያርኮች ስለ ነበሩ ነው:: ቅዱስ ዼጥሮስ ቀዳማዊ 'ተፍጻሜተ ሰማዕት' [የሰማዕታት ፍጻሜ] የተባለው ሲሆን ፲፯ኛ ሊቀ ዻዻሳት ነው::
ቅዱስ ዼጥሮስ ካልዕ ደግሞ በ፫፻፸ዎቹ አካባቢ ፳፩ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ የተሾመና የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ደቀ መዝሙር የነበረ አባት ነው:: ዛሬ የምናስበው አባ ዼጥሮስ ደግሞ በ470ዎቹ አካባቢ ሊቀ ዽዽስናን በግብጽ ተሹሞ ያገለገለውን ነው::
ወቅቱ መለካውያን [የኬልቄዶን ጉባኤ አማኞች] የሰለጠኑበት በመሆኑ ሁኔታዎች ትንሽ አስቸጋሪ ነበሩ:: አንደኛ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ፪ የተከፈለችበት ጊዜ በመሆኑ ፈተናው ለእረኞች ቀላል እንዳይሆን አድርጐታል:: ሌላውና ዋናው ፈተና ግን በዘመኑ የነበሩ ነገሥታት ለመለካውያን [ለመናፍቃን] ወግነው ምዕመናንን ማሳደዳቸው ነው::
አባ ዼጥሮስ ከተመረጠ በኋላ አስቀድሞ ያደረገው አጋዥ መፈለግ ነበር:: እግዚአብሔር ሲረዳው የታላቂቱ ሃገር የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ የሆነው ቅዱስ አካክዮስን አገኘ:: ከእርሱ ጋርም ደብዳቤ ይጻጻፉ ያዙ::
ደብዳቤ ሲባል ግን እንዲህ እኛ በዘመኑ እንደምንጽፈው ያለ አይደለም::ይልቁን ፭ቱ አዕማደ ምሥጢራትን የተሞሉ ጦማሮች ነበሩ እንጂ:: ፪ቱ አበው በየሃገራቸው እየዞሩ እየሰበኩ: አልደርሱበት ባሉበት ቦታ ደግሞ ክታቦችን እየጻፉ በአንድነት ስለ ቀናች ሃይማኖት ደከሙ::
በእግዚአብሔር ቸርነትም ተሳካላቸው:: አባ ዼጥሮስ በዚህች ቀን ሲያርፍ መሰሉ 'ካልእ አትናቴዎስ' ተክቶታል:: ከፈጣሪውም እሴተ ኖሎትን [የእረኝነት ዋጋውን] ተቀብሏል::
አምላከ አበው ዻዻሳት መንጋውን በርሕራሔ የሚጠብቁ እረኞችን ያድለን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
[ ኅዳር ፪ [ 2 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. አባ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ሣልስ
፪. አባ ሱንቱዩ ሊቀ ዻዻሳት
፫. ቅድስት ሴቴንዋ ነቢይት
፬. ቅድስት አንስጣስያ
[ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪. ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫. ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬. ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ [ታላቁ]
፭. ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፮. አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
፯. ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ [ከ፲፪ቱ ሐዋርያት]
🕊
"ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና:: ወንጌልን ብሰብክ እንኩዋ የምመካበት የለኝም:: ግድ ደርሶብኝ ነውና:: ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ:: ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና:: ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል:: እንግዲህ ደመወዜ ምንድን ነው? ወንጌልን እየሰበክሁ በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ብናገር ነው::" [፩ቆሮ.፱፥፲፭]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 እርሷ የሕይወት በር ናት ! 🕊 ]
❝ ኩላዊት ቤተ ክርስቲያን በዓለሙ በሙሉ የተቀበለችው እምነት አንድ ነው፡፡ ስለዚህ እውነትን ከራሳችን ቤተ ክርስቲያን እንጂ ከሌሎች መፈለግ አይኖርብንም።
ሐዋርያት ገንዘቡን በባንክ እንዳስቀመጠ ሀብታም ሰው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስቀምጠውልናል፡፡ ከዚህ መዝገብ የሚፈልግ ሁሉ ከሕይወት ውኃ እየቀዳ ገንዘቡ ሊያደርገው ተፈቅዶለታል:: ውርሱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፤ ኑዛዜው የመድኅን ክርስቶስ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ሐዋርያት ፣ አሰረ ፍኖታቸውን ተከትለው የተጓዙ ሐዋርያነ አበውና ሊቃውንት ሁሉ ነው፡፡
እርሷ የሕይወት በር ናት። ሌሎች ሌባና ወንበዴዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በእውነተኛ ትምህርታችን ልናስወግዳቸው ያስፈልጋል። ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ የሆነውን ነገር እንመርጣለን፡፡ እርሱም እውነትን ገንዘብ የማድረግ በርሱም የመጓዝ ትውፊት ነው:: ❞
[ ቅዱስ ሄሬኒዎስ ]
💖 🕊 💖
🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። †
† ኅዳር ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †
🕊 † ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ † 🕊
ሃገራችን ኢትዮዽያ በሁሉም ዘርፍ ቅድስና ያላቸው ቅዱሳን ባለቤት ናት:: በዘመኑ ያለን ወጣቶችም ሆነ ጐልማሶች ከቤተ ክርስቲያንና ከቅድስና ሕይወት ለምን እንደራቅን ስንጠየቅ ከምንደረድራቸው ምክንያቶች አንዱ ሥራችን ነው::
ነገር ግን ሥራው በራሱ ኃጢአት እስካልሆነ ድረስ በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ቢሆን ቅድስናን ማስጠበቅ እንደሚቻል አበው አሳይተውናል:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም ከእነዚህ ቅዱሳን አንዱ ነው::
- እርሱ ንጉሥ ነው: ግን ገዳማዊ ሕይወትን በቤተ መንግስቱ ውስጥ ያሳየ ጻድቅ ነው::
- ሁሉ በእጁ ነው: እርሱ ግን ንጹሕና ድንግል ነው::
- እርሱ የጦር መሪ ነው: ግን በእጁ ደም አልፈሰሰም::
- እርሱን 'ወደድንህ: ሞትንልህ' የሚሉ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ነበሩት:: ለእርሱ ግን ፍቅር ማለት ክርስቶስ ነበር::
- የሃገር መሪ: የኢትዮዽያ ንጉሠ ነገሥት እንደ መሆኑ እጅግ ባተሌ [busy] ነው:: ግን ደግሞ ለክርስትናው ጊዜ ያጣ ሰው አልነበረም::
እኛ ቤተ ክርስቲያንን "በሐኪ" ለማለት [ለመሳለም] እንኳ 'ጊዜ የለኝም' ስንል እርሱ ግን አብያተ ክርስቲያናትን ይፈለፍል: ያንጽ: በክህነቱ ያገለግል: ማዕጠንት ያጥን: ለረጅም ሰዓትም ይጸልይ ነበር::
እኛ 'ሥራ ውያለሁና ደክሞኛል' ብለን ከስግደት ስንርቅ እርሱ ግን ንጉሥ ሆኖ ሳለ: ጦር በፊት: በኋላ: በቀኝና በግራ ተክሎ ይሰግድ ስለ ነበር ደሙ እንደ ውሃ በምድር ላይ ፈሷል:: ይህንን ሁሉ ያደረገው ቅዱሱ የኢትዮዽያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ነአኩቶ ለአብ ነው::
"ለመሆኑ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ማን ነው?"
ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግስት ከነገሡ ፲፩ ነገሥታት አንዱ ሲሆን ከመጨረሻውም ፪ኛ ነው:: እርሱን በ፲፪ኛው መቶ ክ/ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ [ገብረ ማርያም] እና መርኬዛ ናት:: ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው::
እናቱ መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጀሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር:: ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ [ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ] ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች:: ሕጻኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ "ነአኩቶ" እያለ ሲዞር ሰማችው::
እዚያው ላይም 'ነአኩቶ ለአብ' [አብን እናመስግነው] ስትል ስም አወጣችለት:: ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግስቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በርሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕጻን ወደ አጐቱ ላሊበላ ቤተ መንግስት ውስጥ ገባ::
የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከርሱና ከሚስቱ [ቅድስት መስቀል ክብራ] ሕጻኑ ነአኩቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ:: በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና:: ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም እድሜው ፴ ደረሰ::
በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ:: ቅዱሱ ነአኩቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት:: ቤተ መንግስቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ::
በውስጡም በ፬ አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው:: ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር: ቅዳሴ ሲቀድስ: በጾም ይውላል:: ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቁዋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል::
ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል:: ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል:: እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል:: በተለይ ዐርብ ዐርብ ሲሆን ደሙ: እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር:: እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና::
ከተጋድሎው ጐን ለጐን ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር:: በተለይ በ፲፪፻፲፩ አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት:: እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግስቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት: ይቀድስባትም ነበር::
ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ሥውራን ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ:: እርሱም "ወገኖቼ! ከወዴት መወጣችሁ?" ቢላቸው "መዐዛ እጣንህን አሽተን መጣን" ሲሉ መለሱለት:: በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ "አሽተን [አሸተን] ማርያም" ስትባል ትኖራለች::
ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የነገሠ በ፴ ዓመቱ ነው:: ለ፵ ዓመታት በእንዲህ ያለ ቅድስና ኑሮ ፸ ዓመት ሞላው:: በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ሰላምታንም ሰጠው::
"ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለ፵ ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም:: ከፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና:: የሚያከብርህን አከብረዋለሁ:: ደጅህን የሳመውን: ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን: መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው::
ቀጥሎም "ይሕች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር" አለው:: እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጸበል ይንጠበጠባል:: ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን:: ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና::
ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደውታል:: የተሰወረበትን ዕለት ስንክሳር ሕዳር ፩ ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በ፫ ነው ይላሉ:: በዙፋኑም ላይ የአጐቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል::
አምላከ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በቃል ኪዳኑ ይማረን:: ከበረከቱም አትረፍርፎ ይስጠኝ::
🕊
[ ኅዳር ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፪. ቅዱሳን መክሲሞስና ባልንጀሮቹ [ሰማዕታት]
[ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
፬. ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፭. ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
"ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን: ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን:: ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን::" [ሮሜ.፮፥፭]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 ድምፀ ተዋሕዶ 🕊 ]
🍒▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬🍒
[ ሕይወት የሚገኝባቸው የቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርቶች በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በድምፅ ይቀርባሉ። ]
[ ሳምንታዊ መርሐ-ግብር ]
🕊
❝ የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ፤ ነፍስን ይመልሳል ፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል።
የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው ፥ ልብንም ደስ ያሰኛል ፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው ፥ ዓይንንም ያበራል። ❞
[ መዝ . ፲፱ ፥ ፯ ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
[ ❝ የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ! ❞ ]
[ ክፍል - ፴፪ - ]
💖 ድንቅ ትምህርት 💖
[ በመምህራችን በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ ]
❝ የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል። ❞ [ ምሳ.፩፥፴፫ ]
† † †
▬▬▬▬ ▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬
👇
†
🕊 [ መጥምቀ መለኮት ] 🕊
▬▬▬▬▬▬▬💖▬▬▬▬▬▬
🕊
❝ ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች ፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። ❞ [ ማቴ. ፲፩፥፲፪ ]
[ ዮሐንስ መጥምቅ ማስተማር ከጀመረበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማይ ወንጌል የሚቀበላት አጥታ ትበደላለች፡፡ ወግፉዓን ይትማሰጥዋ፡፡ [ የተገፉ የተበደሉ ግን ይናጠቋታል፡፡ ] ]
† 🕊 የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች 🕊 †
+ ነቢይ
+ ሐዋርያ
+ ሰማዕት
+ ጻድቅ
+ ካሕን
+ ባሕታዊ / ገዳማዊ
+ መጥምቀ መለኮት
+ ጸያሔ ፍኖት [ መንገድ ጠራጊ ]
+ ድንግል
+ ተንከተም [ የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ ]
+ ቃለ አዋዲ [ አዋጅ ነጋሪ ]
+ መምሕር ወመገሥጽ
+ ዘየዐቢ እምኩሉ [ ከሁሉ የሚበልጥ ]
🕊
ይህች ዕለት ለቅዱሱ 'አስተርዕዮተ ርዕሱ' ወይም ቅድስት ራሱ ከተወረችበት የተገለጠችበት ነው::
የቅዱስ ዮሐንስ የጸሎቱ ኃይል የምልጃዉ በረከት ዘወትር በምንማጸነዉ ልጆቹ ላይ አድሮና ጸንቶ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።
† † †
🌼 🕊 🌼
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ከዚሕ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ፲፭ ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::
ይህች ዕለት ለቅዱሱ 'አስተርዕዮተ ርዕሱ' ወይም ቅድስት ራሱ ከተወረችበት የተገለጠችበት ነው::
🕊
ጥቅምት ፴ [ 30 ]ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩. ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
፪. ቅዱስ አርስጥቦሎስ [አባቱ]
፫. ቅድስት ማርያም [እናቱ]
፬. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፭. አባ አብርሃም ገዳማዊ
፮. ቅዱስ ይስሐቅ ንጉሥ
ወርኃዊ በዓላት
፩. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፪. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፫. አባ ሣሉሲ ጻድቅ
" ... እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ:: ዼጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሏት አንዲት አገልጋይ ትሰማ ዘንድ ቀረበች:: የዼጥሮስ ድምጽ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሳ ደጁን አልከፈተችም:: ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ዼጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች::" [ሐዋ.፲፪፥፲፪-፲፭]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 እናታችን ማርያም 🕊 ]
" ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት ፥ እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።"
[ ፲፱፥፳፭-፴ ]
🕊
[ ጻድቅ ሰው ፍርድ ሲመለስ ባየ ጊዜ ደስ እንዲለው ፤ ጠላትን [ አጋንንትን ] በመበቀል የታምራትሽን ኃይል ግለጪ አሳዪ፡፡ የአምላክ እናት ማርያም አንቺን የሰደበ እንዴት በሕይወት ሊኖር ይገባዋል? በእናት በአባቱ ላይ ክፉ ቃልን የተናገረ በልጅሽ ፍርድ ይሙት ተብሏልና፡፡ (ዘዳ.፳፯፥፲፮) ]
[ አባ ጽጌ ድንግል ]
† † †
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 ገ ድ ለ ቅ ዱ ሳ ን 🕊 ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
[ የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ የተጋድሎ ሕይወቱና ትምህርቱ ]
[ ክፍል ሠላሳ አራት ]
💛
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
[ ድውያንን መፈወሱና ሙት ማስነሣቱ ! ]
🕊
............. በልቡ ይጸልይ ነበር ! ..........
❝ ወደ ቅዱስ መቃርዮስ የተለያዩ በሽተኞችን ከግብጽ ሀገር ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ሀገሮችም ያመጧቸው ነበር፡፡ እርሱም አስቀድሞ ቅዱስ እንጦንዮስ ፦ “ እግዚአብሔር ለአባት መቃርዮስ የመፈወስ ጸጋን ሰጥቶታል ” ብሎ እንደ ተናገረ ሁሉንም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ይፈውሳቸው ነበር፡፡ ሁል ጊዜ በበኣቱ ዙሪያም በሽተኞችና ርኲሳን መናፍስት ያለባቸው ሰዎች አይጠፉም ነበር፡፡ እርሱም እውነተኛ አምላክ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲጸልይላቸው ሁሉንም በሽተኞች ይፈውሳቸውና ርኲሳን መናፍስትንም ያሳድዳቸው ነበር፡፡ ሌሎች የተለያየ በሽታ ያለባቸውንና የአእምሮ በሽተኞችን ሁሉ በኃይለ እግዚአብሔር እየፈወሳቸው እነርሱም እግዚኣብሔርን እያመሰገኑ ወደየ መጡበት ይመለሱ ነበር፡፡ ሙታንንም ያስነሣ ነበር ፤ በአጠቃላይ ቅዱስ መቃርዮስ በአምላኩ ኃይል ሊያደርገው ያልቻለው ነገር አልነበረም፡፡
መስማት የተሣነውንና አንደበቱ ዲዳ የሆነውን ፈወሰው
በአንድ ወቅት ርኲስ መንፈስ ያደረበትንና አንደበቱ ዲዳ የሆነ ምንም የማይናገርን ሰው ወደ እርሱ አመጡት፡፡ ያ ሰውም ከታሰረበት ገመድ በተፈታ ጊዜ በሚያገኘው ሰው ሁሉ ላይ ጉዳት ለማድረስ ያስቸግር ነበር፡፡ ወደ እርሱ ባመጡት ጊዜም ቅዱስ መቃርዮስ ይዘው ያመጡትን ሰዎች ፦ “ ተውት ልቀቁት ” አላቸው፡፡ እነርሱም ፦ “ አባታችን ሆይ ፣ ከለቀቅነውማ በዚህ በተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ላይ ጉዳት ያደርሳል” አሉት፡፡ እርሱም ፦ “ዳግመኛ እኔ የምላችሁን ስሙ ፣ ልቀቁት ” አላቸው፡፡ በለቀቁት ጊዜም ታስሮበት የነበረውን ሰንሰለትና ገመድ ራሱ ፈታው፡፡ ከዚያም በኃይል እየጮኸ ወደ ተራራ ይሮጥ ነበር፡፡ ያመጡት ሰዎችም ቅዱስ መቃርዮስን ፦ " አባታችን ሆይ ፣ እነሆ አሁን ሁላችንንም ሊያጠፋን ነው” አሉት፡፡ እርሱም ፦ “አትፍሩ ኣይዟችሁ” ብሏቸው በልቡ ይጸልይ ነበር። በሽተኛውም በተራራው ላይ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይዘዋወር ነበር፡፡
እንዲያ ከዞረ በኋላ ተመልሶ ወደ ቅዱስ መቃርዮስ መጣ፡፡ አባት መቃርዮስም ፦ “ስምህ ማነው?” አለው ፤ ርኲስ መንፈሱም ፦ “ስሜን ትጠይቃለህን ? ሌጌዎን ነኝ ፣ ብዙዎች ነን” አለው፡፡ ቅዱስ መቃርዮስም ፦ " የሁሉ አምላክ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ከዚህ ሰው ውጣ ፤ ወደ እርሱም መቼም ቢሆን ፈጽመህ አትግባ ፤ አምላኬ እንዲህ ያዝሃልና” አለው፡፡ ያን ጊዜም ያ ሰው መሬት ላይ ተዘረጋ ፣ እንደ ሞተ ሰውም ሆነ፡፡ ቅዱስ መቃርዮስም ጸሎት ያደረገበትን ውኃ በፊቱ ላይ ረጨው፡፡ በጆሮውና በአፉ ላይ በመስቀል ምልክት አማተበ ፣ ከዚያም ትንሽ ይተኛ ዘንድ ተወው፡፡ በዘይት ላይ በመጸለይ ሰውነቱን ቀባውና “ወደ ማደሪያህ ሂድ” አለው:: በተነሣ ጊዜም ከደዌው ሁሉ ተፈውሶ መስማትና መናገር የሚችል ሆነ ፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግን ነበር፡ ፡ ❞
የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃና ጸሎቱ አይለየን፡፡
ይቆየን !
† † †
💖 🕊 💖
" በእሸቅድምድም ሥፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንዲሮጡ: ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ:: የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል:: እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው:: እኛ ግን የማይጠፋውን::" [፩ቆሮ.፱፥፳፬]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 መላእክት ሁሉ ይዘምሩላታል 🕊 ]
🌼▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬🌼
❝ በሰማያት ኵሎሙ መላእክት ይኬልልዋ… ወበምድርኒ ኵሎሙ ቅዱሳን ይቄድስዋ... እስመ ወለደት ወልደ ዘበኵራ ያፈቅርዋ እንዘ ንጽሕት በድንግልና… አልባቲ ሙስና ፤ ❞
ትርጉም ፦ በሰማያት መላእክት ሁሉ ይዘምሩላታል ፣ … በምድርም ቅዱሳን ሁሉ ያመሰግኗታል ፣ … በድንግልናዋ ንጽሕት ስትሆን የበኵር ልጇን ወልድን ስለወለደች ይወዷታልና ፣ … እሷ ርኵሰት የሌለባት ናት"
🕊
[ ድጓ ዘክረምት ]
† † †
💖 🕊 💖
†
[ 🕊 ገ ድ ለ ቅ ዱ ሳ ን 🕊 ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
[ የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ የተጋድሎ ሕይወቱና ትምህርቱ ]
[ ክፍል ሠላሳ ሦስት ]
💛
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
[ አጋንንት ዳግመኛ በእርግናው ወራት አባ መቃርዮስን ሊፈትኑት መጡ ! ]
🕊
ባወቀባቸው ጊዜ ዝም እላቸው ! .....
❝ ድካም እየተጫጫነው እየሄደ እያለ በእንድ ወቅት በበኣቱ ውስጥ ሳለ ሰይጣናት ምጽዋትን በሚለምኑ ሰዎች አምሳል ሆነው ፦ " ምጽዋት ትሰጠን ዘንድና ምሕረትን ታደርግልን ዘንድ እንለምንሃለን " እያሉ የበኣቱን በር አንኳኩ ፣ እርሱም ነግራቸውን ባወቀባቸው ጊዜ ዝም እላቸው ምንም ቃል አልመለሰላቸውም፡፡
እነርሱም እርስ በእርሳቸው “ ተኝቷል ! እንቅልፍ ዓይኑን አክብዶታል ፣ ሞቶልን በሆነ ባረፍንና ከእርሱ በተገላገልን ነበር " ይሉ ነበር፡፡ እርሱ ግን ነፍሱ በእግዚአብሔር የጸናች ንቅህት ነበረችና እነርሱ የሚያደርጉትን ከንቱ የሆነ እሳሳችና ምትሃታዊ ድርጊት እንደ ኢምንት ቆጠረባቸው፡፡ሰይጣናቱም ፦ “ ሞቶ ከሆነ ከብዙ ተጋድሎው እናርፋለን ፤ ከእርሱ ሞት በኋላ ይህን የመነኰሳት ማኅበር እንበትነዋለን ፣ ይህን ገዳምም ከእነዚህ መነኰሳት ነጻ እናደርገዋለን ፣ እነርሱ ወደዚህ ከመምጣታቸው በፊት እንደ ነበረው ማድረግ አለብን” አሉ፡፡
ቅዱስ መቃርዮስም እንዲህ ሲሉት ይሰማቸው ነበርና እሳፈራቸው ፤ በአርምሞው ዘለፋቸው ጸሎቱን ያለ ማቋረጥ በመጸለይ ችላ ባላቸውና ባሳፈራቸው ጊዜ ታወኩ ፤ ተረበሹ፡፡ ከዚያም የበኣቱን በር በድንጋይ ይሰብሩ ዘንድ ተነሡ ፡ በዚህም ነፍሱ አልተናወጸችም ዳግመኛም ድንጋይ አነሡና ከወደ ውጭ ይደበድቡት ጀመር፡፡ ሆኖም እግዚኣብሔር ከእነርሱ ስለ ሰወረው ከእነርሱ አንዳች ጥፋት አላገኘውም፡፡ እርሱ አሁንም በአርምሞ ሆኖ ዝም ብሎ ይመለከታቸው ነበር፡፡ እነርሱ የሚወረዉሩት ድንጋይም ወደ ራሳቸው እየተመለሰ የአንዱ ድንጋይ ሌላውን የሚመታው ሆነ፡፡ እነርሱም ምንም እንደማይመልስላቸው ባዩ ጊዜ እነሆ መቃራ በእውነት ሞቷል" እያሉ በመሞቱ እጅግ ደስ እያላቸው ይጮኹ ጀመር፡
ቃላቸውን ከፍ አድርገው አኃው እስኪሰሟቸውና ምን እንደ ሆነ መጥተው እስኪያዩ ድረስ በኃይል እልል ይሉ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ አረጋዊ ቅዱስ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ተነሣና “እግዚአብሔር ያሳፍራችሁ ፣ ከምድር ሁሉ ያውካችሁ” አላቸው:: ቃሉን በሰሙ ጊዜ እንዳልሞተ አወቁ፡፡ ያን ጊዜ ትቢያ ከመሬት ላይ እያነሡ ወደ አየር እየበተኑ “ ሽምግልናህ የከፋ ክፉ የሆንክ አረጋዊ ፣ አንተ በእኛ ላይ በርትተህብናል ፣ አሸንፈኸናልም ” አሉ፡፡ እርሱም በጌታ ስም ገሠጻቸው ፤ እነርሱም እንደ ብዙ አንበጣ ሆነው በደመና አምሳል እየበረሩ
ሄዱ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ቅዱስ መቃርዮስን ከሰይጣናት ፈተናና ከተንኮላቸው ሁሉ ያሳርፈው ዘንድ ወደደ፡ ፡ እርሱም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዕረፍትና በጸጥታ ልብ መኖር ጀመረ ፤ ከዚህ ዓለም እስከሚሄድበት ጊዜ ድረስም ከዚያ በኋላ ከኃዘናትና ከፈተናዎች አንድም እንኳ ያውከው ዘንድ አልመጣበትም፡፡ እርሱ ግን ኃዘናትና ፈተናዎች የሚመጡበት እየመሰለው ይጠባበቅ ነበር፡፡ ስለዚህም ሁል ጊዜ ልክ ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ እርግናው ያደርግ እንደ ነበረው ልቡ ንቁህ ነበር፡፡ ❞
የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃና ጸሎቱ አይለየን፡፡
ይቆየን !
† † †
💖 🕊 💖
🕊
[ † እንኳን ለጻድቁ አቡነ ይምዓታ እና ለአበው ቅዱሳን መርትያኖስ ወመርቆሬዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
† 🕊 አባ ይምዓታ ጻድቅ 🕊 †
† ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት:: አባ ይምዓታ ከዘጠኙ [ተስዓቱ] ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::
ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር :-
፩. የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ::
፪. ዓላማ [የእግዚአብሔር መንግስት] እና
፫. ገዳማዊ ሕይወት ነው::
አባ ይምዓታን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::
በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::
በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ፬፻፸ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::
ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ "ቤተ ቀጢን" ትባላለች::
አባ ይምዓታና ፰ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር::
ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ ይምዓታ እንደ ገና አቀጣጠሉት::
ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::
ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ ይምዓታ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::
የነ አባ ይምዓታ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::
- ዸንጠሌዎን በጾማዕት::
- ገሪማ በመደራ::
- ሊቃኖስ በቆናጽል::
- አረጋዊ በዳሞ::
- ጽሕማ በጸድያ::
- ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::
- አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ [እዛው ትግራይ] ሆነ::
ጻድቁ ወደ ቦታው ሲሔዱ ወንዝ [ባሕር] ተከፍሎላቸዋል:: ወደ ቦታው ደርሰውም ገዳም አንጸዋል:: በቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠርተው በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል:: የአቡነ ይምዓታ ገዳም ገርዓልታ [በፎቶው ላይ እንደምናየው] እጅግ ድንቅና ማራኪ ነው::
ነገር ግን እዛው ድረስ ሒዶ ለማየት ብርታትን ይጠይቃል:: በተራሮች መካከል ከመቀመጡ ባሻገር የአባቶቻችንን ጽናት የሚያሳይ ድንቅ ቦታ ነው:: ጻድቁ በዚሁ በፎቶው ላይ በምናየው ገዳም ለዘመናት ተጋድለው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::
† 🕊 ቅዱሳን መርትያኖስና መርቆሬዎስ 🕊 †
† እነዚህ ቅዱሳን የቁስጥንጥንያ ሰዎች ሲሆኑ የወቅቱ ፓትርያርክ አባ ዻውሎስም ደቀ መዛሙርት ናቸው:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ በአርዮሳውያን ምክንያት ስደት በሆነ ጊዜ አባ ዻውሎስ: ቅዱስ አትናቴዎስ: ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቅዱስ ሊዋርዮስ ከመንበራቸው ተፈናቀሉ::
በስደቱ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሲያርፍ ቅዱሳኑ አትናቴዎስና ሊዋርዮስ ተመለሱ:: አባ ዻውሎስን ግን በእሥር ቤት ውስጥ ሳለ በንጉሡ ትዕዛዝ አርዮሳውያን አንቀው ገደሉት:: ይህንን ያወቁት 2ቱ ደቀ መዛሙርቱ [መርቆሬዎስና መርትያኖስ] ቅዱስ አባታቸውን ቀብረው ንጉሡን ረገሙት::
አርዮሳዊው ታናሹ ቆስጠንጢኖስም ይህንን በሰማ ጊዜ ፪ቱንም አስመጥቶ በአደባባይ በሰይፍ አስመታቸው:: ይህ ከተከናወነ ከ፶ ዓመታት በሁዋላም ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ሆኖ በመምጣቱ ሥጋቸውን አፈለሠ:: ቤተ ክርስቲያንንም አንጾ ቀድሶላቸዋል::
† አምላከ አበው ቅዱሳን በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
🕊
[ † ጥቅምት ፳፰ [ 28 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. አባ ይምዓታ ጻድቅ [ከተስዓቱ ቅዱሳን]
፪. ቅዱሳን መርትያኖስ ወመርቆሬዎስ [ሰማዕታት]
፫. አባታችን ያፌት [የኖኅ ልጅ]
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪. ቅዱሳን አበው [አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ]
፫. ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬. ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
፭. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ [ሰማዕት]
፮. ቅዱስ አባዲርና ቅድስት ኢራኢ
† " በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኩዋ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: " † [፩ዼጥ.፫፥፲፫]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖