gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ታላቁ ቅዱስ ኤልያስ <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች። "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች። እርሱ ሰማይን የለጐመ፣ እሳትን ያዘነመ፣ ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና።
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እስራኤል (አሥሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ ኢያስኑዩ እናቱ ደግሞ ቶና (ቶናህ) ይባላሉ። በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማኅጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ።

ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል። ብርሃን የለበሱ አራት ሰዎች (መላእክት) መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው።

ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእስራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል። ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ንጽሕናንም የሚወድ እስራኤላዊ ነው።

ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት ዘጠኝ መቶ ዓመት በፊት) ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር። ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እስራኤል ገብተው ነበር።

ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር።

በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው። እርሱም "እሺ" ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ። ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ።

በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር። በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ፦
፩.ለድንግልና (ድንግል ነበርና)
፪.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና)
፫.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል።

መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን፣ በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን፣ በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም። በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእስራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት።

ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሐሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት። ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም፤ አልለውጥም።" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል።

ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም። የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል።" አላቸው። በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም።

በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች። ዘጠኝ መቶው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው። በእስራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ። የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ።

ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ፦
"ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል ዘቆምኩ ቅድሜሁ ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ።" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ።

ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ። እርሱን ቁራ ይመግበው ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር። ይሔው ቢቀርበት ጸለየ። እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው። በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ።

ልጇ ሕፃኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት። ቀጥሎም ሰባት ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል። ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል።

ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል ስምንት መቶ ሃምሳ ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል። መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ ስምንት መቶ ሃምሳውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል።

ይህንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው። "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻዬን ቀርቻለሁና።" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው።

ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል) ቀስቅሶ ታየው። እንጐቻ ባገልግል ውኃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው። በላ፣ ጠጣ፣ ተኛ። እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው። በሦስተኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ።" አለው።

ኤልያስም ለአርባ ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል። ከዚያ በኋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም። እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ ሁለት ጊዜ እሳትን አዝንሟል።

የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ።" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን።" አለው። ሦስት ጊዜ ሊያስመልሰው ሞከረ። ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው። ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው። ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት።

ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሄኖክ ጋር ያርፋል።
ለተጨማሪ ንባብ (ከ፩ነገ. ፲፯ - ፪ነገ. ፪ እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ።)

ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው!

አምላከ ኤልያስ ለሃገራችንና ለሕዝቧ ርኅራኄውን ይላክልን።

<3 ጻድቅ ኖኅ <3

የዚህን ታላቅ ቅዱስ ሰው ክብር የሚያውቅና የሚያከብረው ሁሉ ንዑድ ነው። አባታችን ኖኅ ዛሬ በዓለም የሚመላለሰው ሰው ሁሉ አባት ነው። ደግ ጻድቅና ነቢይ ሰው ነው።

ከአባታችን አዳም አሥረኛው ጻድቅ ሲሆን ከአሥራ አምስቱ አበው ነቢያትም አንዱ ነው። ከአባቱ ከላሜሕ ተወልዶ፣ በደብር ቅዱስ አድጐ፣ ንጽሐ መላእክትን ገንዘብ አድርጐ፣ ለአምስት መቶ ዓመታት በድንግልና ኑሯል።

በእነዚህ ጊዜያትም አጽመ አዳምን እየጠበቀና መስዋዕትን ለልዑል አምላክ እየሰዋ ያመልክ ነበር። የሴት ልጆች ከቃየን ልጆች ጋር ተባብረው ዓለም በረከሰች ጊዜም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ ተገኝቷል። ከሚስቱ (እናታችን) ሐይከል (አምዛራ) ጋር ሦስት ጊዜ አብሮ አድሮ ሴም፣ ካምና ያፌትን ወልዷል።

የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜም የእመቤታችን ምሳሌ በሆነች መርከብ ድኗል። ከመርከብ ወጥቶም ከጌታ ጋር በቀስተ ደመና ምስክርነት ቃል ኪዳን ተጋብቷል። ከዚያም ዓለምን ለሦስት ልጆቹ አካፍሎ ለሦስት መቶ ሃምሳ ዓመታት በበጐ አምልኮ ኑሯል። በዚህች ቀንም ዕድሜን ጠግቦ በዘጠኝ መቶ ሃምሳ ዓመቱ ዐርፏል።

የአባታችን በረከት ይደርብን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ግዝረት፣ ለታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ፣ ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤልያስ እና ለጻድቁ ቅዱስ ኖኅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 በዓለ ግዝረት <3

"በዓል" ማለት በቁሙ "ክብር፣ መታሰቢያ" እንደ ማለት ነው። የበዓላት ባለቤት ደግሞ ራሱ እግዚአብሔር ነው። በመጻሕፍተ ኦሪት እንደ ተቀመጠው ጌታ ምርጦቹን (ሕዝቡን) ስለ በዓላት አዝዟል። ከሰንበት ጀምሮ የፋሲካ፣ የእሸት፣ የዳስ.....ወዘተ. በዓላት በብሉይ ኪዳን ይከበሩ ነበር።

በእርግጥ አሕዛብም ለጥፋታቸው በዓላትን ሲያከብሩ ኑረዋል። ዛሬም ቀጥለዋል። በዓላት በሐዲስ ኪዳንም ቀጥለዋል። የቅዱሳን ሐዋርያትና ሊቃውንትን ቀኖናዎች መሠረት አድርጋ ቤተ ክርስቲያን በዓላትን ታከብራለች።

እነዚህም ከጊዜ (ወቅት) አንጻር፦
የሳምንት
የወር እና
የዓመት በዓላት ተብለው ሲታወቁ ከተከባሪዎቹ አንጻር ደግሞ፦
የጌታ
የእመቤታችን እና
የቅዱሳን ተብለው ይከፈላሉ።

ጌታ "በዓላትን አክብሩ።" ያለን ሥራ እንድንፈታ ሳይሆን ለአምልኮው እንድንተጋና የጽድቅ ተግባራትን እንድንከውን ነው። ስለዚህም በበዓላት መልካም ይሠራል እንጂ ተተኝቶ አይዋልም። የጌታችን በዓላቱ አሥራ ስምንት ሲሆኑ ዘጠኙ ዐበይት፣ ዘጠኙ ደግሞ ንዑሳን ተብለው ይታወቃሉ። ሁሉም ለእኛ የድኅንት ሥራ የተፈጸመባቸው ናቸው።

የጌታ ዐበይት በዓላቱ፦
፩.ጽንሰቱ (ትስብእቱ)
፪.ልደቱ
፫.ጥምቀቱ
፬.ዑደተ ሆሳዕናው
፭.ስቅለቱ
፮.ትንሣኤው
፯.ዕርገቱ
፰.በዓለ ጰራቅሊጦስ እና
፱.በዓለ ደብረ ታቦር ናቸው።

ንዑሳን በዓላቱ ደግሞ፦
፩.ስብከት
፪.ብርሃን
፫.ኖላዊ ሔር
፬.ጌና
፭.ግዝረት
፮.በዓቱ (በዓለ ስምዖን)
፯.ቃና ዘገሊላ
፰.ደብረ ዘይት እና
፱.በዓለ መስቀል ተብለው ይታወቃሉ።

ከእነዚህም አንዱ በዓለ ግዝረት ሁሌም በየዓመቱ ጥር ፮ ቀን ይከበራል። መድኃኒታችን ለእኛ ሲል በተዋሐደው ሥጋ ማርያም ሕግን ሁሉ ፈጽሟል። ራሱ 'ሠራዔ ሕግ' እንደ ሆነው ሁሉ 'ፈጻሜ ሕግ'ም ተብሏል።

ለአብርሃም ባዘዘው (ዘፍ. ፲፯፥፱) መሠረትም በተወለደ በስምንተኛ ቀኑ ተገዝሯል። ስሙንም ኢየሱስ (መድኃኒት) ብለውታል።
(ሉቃ. ፪፥፳፩)
ነገር ግን የተገዘረው እንደ ፍጡር በምላጭ (በስለት) ሳይሆን በኪነ ጥበቡ ነው። "ማርያም ግዝር" እንዲሉ አበው። ልደቱ እንደማይመረመር ሁሉ ግዝረቱም አይመረመርም።

ለእኛ ሲል ሁሉን የሆነ መድኃኒታችን ክርስቶስ ለፍቅሩና ለክብሩ ያብቃን። ከበረከተ በዓለ ግዝረቱም አይለየን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥር ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ማቴዎስ
፪.ቅዱስ አውስግንዮስ አረጋዊ (ሰማዕት)
፫.ቅድስት እስክንድርያ
፬.ቅድስት አውስያ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፭.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
፮.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)

"አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ! ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ! አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ! ብርቱ ስለ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣ ክፉውንም ስላሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።"
(፩ዮሐ ፪፥፲፫-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲህ ነው፦
ወንጌላዊ
ሐዋርያ
ሰማዕት ዘእንበለ ደም
አቡቀለምሲስ (ምሥጢራትን ያየ)
ታኦሎጐስ (ነባቤ መለኮት)
ወልደ ነጐድጓድ
ደቀ መለኮት ወምሥጢር
ፍቁረ እግዚእ
ርዕሰ ደናግል (የደናግል አለቃ)
ቁጹረ ገጽ
ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ (ከጌታ ጎን የሚቀመጥ)
ንስር ሠራሪ
ልዑለ ስብከት
ምድራዊው መልአክ
ዓምደ ብርሃን
ሐዋርያ ትንቢት
ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
ኮከበ ከዋክብት.....

በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር።

ቅዱስ ዮሐንስን የወደደ ጌታ በፍቅሩ ይጠግነን። ከእናቱ ፍቅር አድርሶ በሐዋርያው በረከት ያስጊጠን።

ጥር ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ (ፍቁረ እግዚእ)
፪.አባ ናርዶስ ጻድቅ (ዘደብረ ቢዘን)
፫.ቅዱስ ጊዮርጊስ
፬.ቅዱስ ማርቴና

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፪.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

"በጌታ ኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፣ የእናቱም እኅት፣ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፣ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። ጌታ ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን 'አንቺ ሆይ! እነሆ ልጅሽ።' አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን 'እናትህ እነኋት።' አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።"
(ዮሐ ፲፱፥፳፭-፳፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ <3

በሃገራችን እጅግ ዝነኛ ከሆኑ ቅዱሳን አንዱ አባ ሊባኖስ ናቸው። እርሳቸው እንደ ተስዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳንና አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሁሉ ከውጪ ሃገር የመጡ ናቸው።

የነበሩበት ዘመንም አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻና ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ነው። ጻድቁ አባ ሊባኖስን "አባ መጣዕ" እያሉ መጥራት የተለመደ ነው። "መጣዕ" ማለት ኤርትራ ውስጥ የሚገኝና ጻድቁ በተጋድሏቸው የቀደሱት ቦታ ነው።
ጥንተ ታሪካቸውስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
አባ ሊባኖስ ትውልዳቸው ከሮም ታላላቅ ሰዎች ነው። አባታቸው አብርሃም እናታቸው ደግሞ ንግሥት ይባላሉ። በብሥራተ መልአክ ተጸንሰው ስለ ተወለዱ ስማቸውም በዚያው "ሊባኖስ" ተብሏል።

"ሊባኖስ" እመ ብርሃን የተወለደችበት ቅዱስ ሥፍራ ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ "ደጋ" ማለት ነው። ምሥጢራዊ ትርጉሙ ግን ለጻድቅነት ያገለግላል። አባ ሊባኖስ በሃገራቸው ሮም ከወላጆቻቸው ጋር አድገው ለአካለ መጠን ሲደርሱ ከወደ ቁስጥንጥንያ ሸጋ ብላቴና አጭተው አጋቧቸው።

ወጣቱ አባ ሊባኖስ ግን ማታ "ወደ ጫጉላ አልገባም።" ብለው እንቢ አሉ። ለዚያች ሌሊት ብቻ ከአባታቸው ጋር እንዲያድሩ ተፈቀደላቸው። መጻሕፍትን የተማሩ ነበሩና በሌሊት ምን እንደሚያደርጉ ሲያወጡ ሲያወርዱ ቅዱስ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ሦስት ጊዜ "ሊባኖስ" ብሎ ጠራቸው።

"እነሆኝ ጌታዬ!" ቢሉት ከአባታቸው ጐን ነጥሎ እያጫወተ ሳይታወቃቸው ከሮም ግብጽ (ገዳመ ዳውናስ) አደረሳቸው።

በጊዜው ታላቁ ኮከብ ቅዱስ ጳኩሚስ ነበር። አባ ሊባኖስን አስተምሮ አመነኮሳቸው፤ በዓትም ለየላቸው። በዚያ ለተወሰነ ጊዜ እንደቆዩም ቅዱሱ መልአክ መጥቶ "ለዘላለም መጠሪያህ በዚያ ነውና ወደ ኢትዮጵያ ሒድ።" አላቸው።

እየመራም ከግብጽ አክሱም አደረሳቸው። አባ ሊባኖስም በዚያ በዓት ወቅረው ይጸልዩ ጀመር። ጥቂት ቆይተውም ለስብከተ ወንጌል ተሰማሩ። በተለይ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በስብከት ከአክሱም ሸዋ (ግራርያ) ደርሰዋል።

ተመልሰው ወደ አክሱም ሔደው ጠበልን አፍልቀው ነበርና ድውያንን ፈወሱ። ሙትን አስነሱ። በዚህ የቀኑት የአካባቢው ሰዎች ግን "ምትሐተኛ ነህ።" ብለው አባረሯቸው። ጻድቁም ዶርቃ በምትባል ቦታ ለሦስት ዓመታት ሲኖሩ በአክሱም ዝናብ አልዘንብ አለ።

ጥፋታቸው የገባቸው የአክሱም ካህናት ወደ ጻድቁ ሔደው "ይማሩን" ቢሏቸው ዘንቦላቸዋል። አባ ሊባኖስ ግን ወደ ሽዋ ተመልሰው በደብረ አስቦ ለመኖር ቢሞክሩ አልተሳካም። መልአኩም ስሙ የአንተ ማደሪያነቱ ግን የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ነውና ወደ "መጣዕ" ሒድ አላቸው።

እርሳቸውም ወደ መጣዕ (ኤርትራ) ወርደው ታላቅ ገዳም አነጹ። ጠበሎችን አፈለቁ። ብዙ አርድእትንም አፈሩ። በዚያም በቅድስናና በገቢረ ተአምራት ኑረው ጥር ፫ ቀን በመቶ አርባ ዓመታቸው ዐርፈዋል። የላሊበላውን ቤተ አባ ሊባኖስን ጨምሮ በርካታ አብያተ መቃድስ በሃገራችን አሏቸው።

የሕፃናቱና የጻድቁ አምላክ እኛን ይማረን። ከበረከታቸውም ያሣትፈን።

ጥር ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.መቶ አርባ አራት ሺህ ቅዱሳን ሕፃናት
፪.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፫.አባ አሞን መስተጋድል

ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱሳን ካህናት (ዘካርያስና ስምዖን)
፬.አቡነ ዜና ማርቆስ
፭.ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት
፮.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ጻድቅ

"አየሁም እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር። ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም የመንፈስ ቅዱስም ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።
.....ደርዳሪዎችም በገና እንደ ሚደረድሩ ያለ ድምጽ ሰማሁ። በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሊቃውንቱ ፊት አዲስ ምስጋና አመሰገኑ። ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም። ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው። ድንግሎች ናቸውና።"
(ራእ ፲፬፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ዘወትር በማይጠልቅ በብሩህ ፀሐይ ፊት በምድር ዳርቻዎች ሁሉ የስምህ ባለሟልነት የደረሰ የአእላፍ ሰማዕታት አለቃቸው ሰላምታ ለአንተ ይገባል።
ክንፈ ፈጣን ከራድዮን ዖፍ የተባልህ ጊዮርጊስ ሆይ የአፍ እስትንፋስን ተቀብለህና ተሸክመህ ሕማሜን በትን።"
(ሊቁ አርከ ሥሉስ)

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዛሬ (ጥር ፪ ቀን) የታላቁ ቅዱስና ሊቀ ሰማዕታት ማር ጊዮርጊስ የልደት በዓሉ ነው፡፡
የማር ጊዮርጊስ በረከቱ ይደርብን፡፡

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ ሰው ቅዱስ አቤል እና ቅዱስ ቴዎናስ ሊቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አቤል ጻድቅ <3

እግዚአብሔር አዳምን በሰባት ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በኋላ ግን ንስሐ ስለ ገባ "ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው።

አዳምና ሔዋን ከገነት ከወጡ በኋላ ወዲያው ሕገ ሰብሳብን (የወንድና የሴት ሥርዓትን) አልፈጸሙም። ይልቁኑ ለአሥራ አራት ኢዮቤልዩ (ለመቶ (ዘጠና ስምንት) ዓመታት) ንስሐ ገቡ፤ አለቀሱ እንጂ።

አለቃቀሳቸውም እንደኛ በቤተ ፈት ልማድ ሳይሆን "እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ታህል ቦታ በበደላችን አጣን።" እያሉ ነበር። "አልቦቱ ለአዳም ካልዕ ሕሊና ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ" እንዲል።
(መቅድመ ወንጌል)

እውነትን እንነጋገር ከተባለ እኛ ለወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ተገቢውን ክብር እየሰጠናቸው አይደለም። አንደበቱን የከፈተ "አስተማሪ" ሁሉ ኃጢአታቸውን እንጂ ክብራቸውን ሲናገር ሰምቼ አላውቅም። ሌላው ይቅርና ማንም ሰው "ቅዱስ አዳምና ቅድስት ሔዋን" ብሎ ሲጠራቸው ገጥሞኝ አያውቅም።

የሚገርመው ደግሞ እኛ እልፍ አእላፍ ኃጢአትን ተሸክመን እነርሱን ስለ አንዲቷ ኃጢአታቸው ስንወቅሳቸው መዋላችን ነው። በእነርሱ ምክንያት ገነት ብትዘጋ ዳግመኛ የተከፈተችው በፍጹም እንባና ንስሐቸው ነው።

"ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት" እንዲል።
(ቅዳሴ ማርያም)
ጌታን ለሰውነት፣ ለሞት ያበቃው ፍቅረ አዳም መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም።

በዚያውም ላይ አባታችን ቅዱስ አዳም፦
በኩረ ኩሉ ፍጥረት
በኩረ ነቢያት አበው
በኩረ ሐዋርያት ወአርድእት
በኩረ ጻድቃን ወሰማዕት
በኩረ ደናግል ወመነኮሳት የሆነ ደግ ፍጥረት ነው። ስለዚህም ቅዱሳን አዳምና ሔዋንን ልናከብራቸው በእጅጉ ይገባናል።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱሳኑ አዳምና ሔዋን ንስሐቸውን ፈጽመው ተስፋ ድኅነት ከተሰጣቸው በኋላ አብረው አደሩ። በዚያች ሌሊትም ቃየንና ኤልዩድ (ሉድ) ተጸነሱ በጊዜውም ተወለዱ።

አሁንም ድጋሚ አብረው ቢያድሩ ቅዱስ አቤልና መንትያው አቅሌማ ተጸንሰው ተወለዱ። ዓለምም በጊዜው እነዚህ ስድስት ሰዎች ይኖሩባት ነበር። ምንም እንኳ እናታችን ቅድስት ሔዋን ብዙ መንትያዎችን ብትወልድም "ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት።" ያለው የጌታ ቃል ይፈጸም ዘንድ ልጆቻቸውን ማጋባት ነበረባቸው።

የመጀመሪያው የልጆች ጋብቻም በአቤልና በኤልዩድ እንዲሁም በቃየንና በአቅሌማ መካከል እንዲሆን ተወሰነ። አባታችን ቅዱስ አዳም ደግ ነቢይ ነውና ለማራራቅ ሲል ይህንን አደረገ። ነገር ግን በውሳኔው እንደማይስማማ ቃየን ተናገረ።

ምክንያቱ ደግሞ የአቤል መንትያ መልኳ የኔ ብጤ በመሆኗና የእርሱ መንትያ ኤልዩድ ግን እናቷን ቅድስት ሔዋንን የምትመስል ቆንጆ ስለ ነበረች "እኔ መንትያዬን ነው የማገባ።" የሚል ነበር።

አቤል ግን የቱንም ቢሉት ከወላጆቹና ከፈጣሪው ትዕዛዝ የማይወጣ ደግ ሰው ነበር። በጊዜውም መላእክት ባስተማሩት መሠረት ቅዱስ ሰው አዳም ለልጆቹ እርሻንና እንስሳት እርባታን አስተምሯቸው ነበርና ቃየን በግብርና አቤል ደግሞ በበግ እረኝነት (እርባታ) ይኖሩ ነበር።

ቅዱስ ሰው አቤል በቅንነቱና በታዛዥነቱ መንፈሰ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሆነለት። ሁሌም ስንጠራው "ጻድቅ" ብለን ነው። ከጻድቃነ ብሊት (ብሉይ) አንዱ ሲሆን የዚህች ዓለም የመጀመሪያው ሟችና ሰማዕት ለመሆንም በቅቷል።

በሴት ልጅ መልክ ምክንያት በዚህች ዓለም ጥላቻ "ሀ" ብሎ ጀመረ። ምንም ሳያደርገው ቃየን ወንድሙ አቤልን ጠላው። የጥላቻ አባቷ ዲያብሎስ ነውና የእርሱ ዘመድ ሆነ።

ነገሮች ያላማሩት ቅዱሱ አባታቸው ግን በጐ መፍትሔ ሊሆናቸው የቀናውንም ሥርዓት ሊያስተምራቸው "ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቅርቡ። እግዚአብሔር መሥዋዕቱን የተቀበለለት ኤልዩድን ያገባል።" አላቸው። "እሺ" ብለው መካነ ምሥዋዕ አዘጋጁ።

አቤል ከንጹሕ ልቡ እንዲህ አሰበ። "እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ንጹሕ ነገርን ይወዳል።" አለ። በዚህም ቀንዱ ያልከረከረውን፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረውን፣ ጠጉሩ ያላረረውን፣ የአንድ ዓመት ነውር የሌለበትን ጠቦት አቀረበ።

ቃየን ደግሞ ከክፉ ልቡ እንዲህ አሰበ። "እግዚአብሔር አይበላ፤ አይጠጣ። ጥሩ ነገር ብሰጠውስ ምን ያደርገዋል።" ብሎ ዋግ የመታውን፣ ነቀዝ የበላውን እሕል (ሥርናይ) አቀረበ። እዚህ ላይ አንድ ነገርን ልብ እንበል።

እግዚአብሔር እንደ ሰው አይበላም፤ አይጠጣም። ይህ እውነት ነው። ግን እግዚአብሔር የአቤልን መሥዋዕት የተቀበለው በጉን ፈልጐ ወይ አቤል ቆንጆዋን ሴት እንዲያገባ አይደለም። ምክንያቱም አቤል እንደሚገደልና በድንግልናው እንደሚሰዋ እርሱ ያውቃልና።

ይልቁኑ እግዚአብሔርን የሚያስደስተው የስጦታው ምንነት ሳይሆን የሰጭው ማንነት ነውና እኛ እንክርዳድ ሆነን ለእግዚአብሔር ስንዴ ልናቀርብለት አንችልም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእኛ ምንም ነገርን አይሻም። ሰማይና ምድር፣ ፍጥረታት በሙሉ የእርሱ ናቸውና።

ንጹሐ ባሕርይ ጌታ ከእኛ አንዲት ነገርን ብቻ ይሻል። ይህቺም በንጹሕ ልቡና የምትቀርብ ንጹሕ አምልኮ ናት። በዚህም የምንጠቀመው እኛ እንጂ እርሱ አይደለም።

ሁለቱ ወንድማማቾች መሥዋዕትን ሲያቀርቡለትም "ወነጸረ እግዚአብሔር ላዕለ አቤል ወላዕለ መሥዋዕቱ" እንዲል እግዚአብለሔር ቃየንና መሥዋዕቱን ትቶ መጀመሪያ ወደ አቤል ቀጥሎም ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ። ማለትም አቤልና መሥዋዕቱን ወደዳቸው።

በዚህ ምክንያትም ቃየን ተበሳጨ። ክፋትን እያሰበ ሲመላለስም ሰይጣን ተገናኝቶ ክፉውን መከረው። በቁራ ተመስሎ ነፍሰ ገዳይነትን አስተማረው። በዚህም ወደ ምድረ በዳ ወስዶ በድንጋይ ጭንቅላቱን መትቶ ገድሎት ሔደ።

በዚህ ምክንያትም አቤል "በኩረ ምውታን - የመጀመሪያው ሟች" ተባለ። "የዋሕ" የተባለበትም ምሥጢሩ ቂም እንደ ያዘበት ክፋትን እንዳሰበበት እያወቀ እንደ በግ ተከትሎት መሔዱ ነው።

ስለዚህም ነገር ለመድኃኒታችን ክርስቶስ ምሳሌው ሆነ። አባ ሕርያቆስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት "የውሃቱ ለአቤል ዘተቀትለ በአመጻ - በአመጻ የተገደለ የአቤል የውሃቱ፣ የየዋህነቱን ዋጋ የምታሰጭው አንቺ ነሽ።" ብሏል።

ቅዱስ አቤል ከተገደለ ከሃያ ስምንት ዓመታት በኋላ ነፍሱ ገነትን ተሳልማለች። ስለ ቅዱሱ ግፍም እግዚአብሔር የቃየንን ዘሮች በጥፋት ውኃ ደምስሷቸዋል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት እና ለአክሚም ሰማዕታት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት <3

በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው። ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እስራኤላውያን አንዱ ነበር።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ። (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ።) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ገባ። የወቅቱ ታላቅ መምህር ገማልያል ይባል ነበር። ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፭፥፴፫ ላይ ተጠቅሷል።

በትውፊት ትምህርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን፣ ጳውሎስን፣ ናትናኤልን፣ ኒቆዲሞስን.....) አስተምሯል። በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር። በፍጻሜውም አምኗል።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ። ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር።

በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ። ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ። ለስድስት ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ።

ለስድስት ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ። በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምህሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው።

"ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው።" በሚል ላከው። ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ እጅ ነስቶ ተማረ።
(ሉቃ. ፯፥፲፰)
በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ። ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው። አጋንንትም ተገዙለት።
(ሉቃ. ፲፥፲፯)

ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ። ምሥጢር አስተረጐመ። ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል።

በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ጵጵስናን) ተሹሟል። በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት ምሥጢርም የተገለጠለት የለም። በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ።

በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ሰባት ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር። አልፎም የስድስቱ ዲያቆናት አለቃ እና የስምንት ሺህው ማኅበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል።

ስምንት ሺህ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው። አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው። መጽሐፍ እንደሚል ግን "መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ማሕደረ እግዚአብሔር" ነውና ለእርሱ ተቻለው።
(ሐዋ. ፮፥፭)

አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ "ሊቀ ዲያቆናት" ሲባል እንደ ዘመኑ ይመስለን ይሆናል። እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው። ዲቁናው ለእርሱ "በራት ላይ ዳረጐት" ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም።

ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ስምንት ሺህውን ማኅበር እየመራ ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት "እጠፋ እጠፋ" ወንጌል ደግሞ "እሰፋ እሰፋ" አለች። በዚህ ጊዜ "ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው።" ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት።

እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው። በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት። ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት።

ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር። ስሙም ሉክያኖስ ይባል ነበር። በተደጋጋሚ በራእይ ቅዱሱ እየተገለጠ "ሥጋዬን አውጣ።" ይለው ነበርና ሒዶ ለጳጳሱ ነገረው። ጳጳሱም ደስ ብሎት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ ገማልያል (የመምህሩ ርስት ነው።) ሔደ።

ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ። መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ። ዝማሬ መላእክትም ተሰማ። ሕዝቡና ጳጳሱም በቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው በታላቅ ዝማሬና በሐሴት ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው በጽርሐ ጽዮን (በተቀደሰችው ቤት) አኖሩት።

እለ እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ ክርስቲያን አንጾለት ወደዚያ አገቡት። ከአምስት ዓመታት በኋላም እለ እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን ስለ ፍቅሩ አኖሩት። ሚስቱ ወደ ሃገሯ ቁስጥንጥንያ ስትመለስ የባሏ ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው።

መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው። እጅግ ደስ አላት። አምላክ ለዚህ አድሏታልና። እርሷም ወስዳ ለታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አስረከበች። በከተማውም ታላቅ ሐሴት ተደረገ።

ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች። በዚያም ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል። ቅዱስ እስጢፋኖስ "ሲመቱ" ጥቅምት ፲፯ ፣ "ዕረፍቱ" ጥር ፩ ፣ "ፍልሠቱ" ደግሞ መስከረም ፲፭ ቀን ነው።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃን ወገዳማውያን አባ ዮሐንስ፣ አባ ዘካርያስ ወአባ ዮሐንስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ዮሐንስ ዘአስቄጥስ <3

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው። በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል። ሕይወቱ በጐላ በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው።

ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ፣ እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል።

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለአርባ ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል፤ አስተምሯል። በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት።

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። አኗኗራቸውም በቡድንም በነጠላም ሊሆን ይችላል።

ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው። ይህም ሲያያዝ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደረሰ። በዚህ ዘመን ግን አባ ጳውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይህንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው። ለሰማንያ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ። ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ።

ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት። በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ። ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ።

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል። ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል።

አባ እንጦንስ አባ መቃርስን፣ አባ መቃርስ አባ ዮሐንስን ወልደዋል። አባ ዮሐንስም የታላቁ ገዳመ አስቄጥስ አበ ምኔት ሆነው በጸጋ አገልግለዋል። አስቄጥስ በምድረ ግብጽ የሚገኝ በስፋቱና ብዙ ቅዱሳንን በማፍራቱ ተወዳዳሪ የሌለው የዓለማችን ቁጥር አንድ ገዳም ነው።

ሕይወተ ምንኩስናም ወደ መላው ዓለም የተስፋፋ በዚህ ገዳም መናንያን አማካኝነት ነው። በዚህ ገዳም ላይ የሚሾሙ አበው ደግሞ በብዛት መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸውና አባታቸውን ቅዱስ መቃርስ ታላቁን የመሰሉ ናቸውና ኃላፊነቱ እጅግ ከባድ ነው።

በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ተወልደው ያደጉት አባ ዮሐንስ ከመነኑባት ዕለት ጀምረው በፍጹም ተጸምዶና ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ስለ ተገዙ የታላቁ ገዳም አበ ምኔት ሊሆኑ ተገባቸው።

በአበ ምኔትነት ዘመናቸውም መንጋውን ይጠብቁ ዘንድ ብዙ ደከሙ። በተለይ ቅዱስ ቃሉን ያስተምሩ ዘንድ ተጉ። ሕይወተ መላእክትንም ያሳዩ ዘንድ በቃል ብቻ ያይደለ በተግባር ሆነው ከመንፈሳዊ አብራካቸው ብዙ ቅዱሳንን ወለዱ።

ከዋክብቱ አባ ገዐርጊ፣ አባ አብርሃም፣ አባ ሚናስ፣ አባ ዘካርያስ..... የአባ ዮሐንስ ፍሬዎች ናቸውና። ጻድቁ በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል። ከዕረፍታቸው በኋላ እንኳ መግነዛቸውና የልብሳቸው እራፊ ብዙ ድውያንን ፈውሷል።

አንድ ጊዜም ለልጆቻቸው መነኮሳት ቤዛ ሆነው በበርበር (አረማውያን) ተማርከዋል። በዚያም ክፉዎች ባሪያ ቢያደርጓቸው እግዚአብሔር ድንቅን ሠርቶ ወደ ገዳማቸው መልሷቸዋል። ከብዙ ተጋድሎ በኋላም በዘጠና ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈው በበዓታቸው ተቀብረዋል።

<3 አባ ዘካርያስ ገዳማዊ <3

ይህም ቅዱስ የተነሳው በዚያው በዘመነ ጻድቃን ነው። ምንም ክርስቲያን ቢሆንም በቀደመ ሕይወቱ ገንዘብ የሚጥመው ነጋዴ ነበር። በንግድ ሥራውም ሃብታም መሆን ችሎ እንደ ነበር ዜና ሕይወቱ ይናገራል።

እግዚአብሔር ሁሉም የሰው ልጆች ወደ መንግሥተ ሰማያት ቢገቡ መልካም ፈቃዱ ነው። ያ ብቻ አይደለም። ለእያንዳንዱ ሰው የድኅነት ጥሪን በተለያየ መንገድ ያቀርብለታል። ድምጹን ለሰማ ወደ ወንጌል ወደብ ያደርሰዋል።

አንዳንዴ "እንቢ" ስንለው እንደ በጐ አባትነቱ በተግሣጹ ሊጠራንም ይችላል። ተግሣጹም በደዌ፣ በአደጋና በመሰል መንገዶች ሊሆን ይችላል። ዋናው ቁም ነገር ግን ጊዜው ሳያልፍብን ቀኑም ሳይመሽብን ድምጹን መስማት፣ ለቃሉ መታዘዝ፣ ጥሪውንና ተግሣጹን አለማቃለል ነው።

አባ ዘካርያስም የቅድስና ሕይወት ጥሪ የደረሰው ለሥጋ ገበያ ሲታትር ነበር። አንድ ቀን ንብረቱን ይዞ ለንግድ መንገድ ላይ ሳለ ሽፍቶች ያዙት። ሊያርዱት አጋድመውት ሳለ ግን የገዳመ ጳኩሚስ አበ ምኔት በሥፍራው ነበርና ጮኸባቸው።

ቅዱሱ አበ ምኔት አካሉ በገድል ያለቀ ቢሆንም ድምጹ እንደ ነጐድጓድ ሲመጣ ገዳዮቹ ደንግጠው በረገጉ። ዘካርያስም ከሞት ተረፈ። እንደ ገና ሃብቱን ይዞ ወደ ከተማ ሲገባ በሃገረ ገዢው ተይዞ ሞት ተፈረደበት። ከገንዘቡ መብዛት የተነሳ ዘራፊ መስሏቸው ነበርና። በዚህ ጊዜም እግዚአብሔር በመኮንኑ ልብ ርኅራኄን ጨምሮ አዳነው።

በዚያች ሌሊት ግን ነገሮችን ያስተዋለው ዘካርያስ የተፈጠሩት አጋጣሚዎች የፈጣሪው ጥሪ እንደ ሆኑ አስተዋለ። ወዲያውም ለዓይነ ሥጋ የሚያሳሳውን ያን ሁሉ ንብረቱን መጽውቶ በርሃ ገባ። በደብረ አባ ጳኩሚስም መንኩሶ በዓት ወሰነ።

ከዚያች ቀን ጀምሮም በፍጹም አምልኮ፣ በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን እያገለገለ ከርኩሳን መናፍስት ጋር ታገለ። በእግሩም ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ቅዱሳት መካናትን ተሳለመ። አንድ ጊዜም ሰይጣን ሰው መስሎ "አባትህ ሳልሞት ልየው እያለህ ነው።" አለው። ውስጡ ግን ፈቃደ ሥላሴ ነበረበትና "እሺ" ብሎ ሒዶ አባቱን ቀብሮ ተመልሷል።

ቅዱስ አባ ዘካርያስ ከብቃቱ የተነሳ የሚኖረው ከግሩማን አራዊት ጋር ነበር። ሁሉንም አራዊትም ይመግባቸው ነበር። በተለይ ደግሞ ዘንዶዎች ሰውን እንዳይጐዱ አዝዞ እርሱ ይመግባቸው ነበር። የተጋድሎ ዘመኖቹን ከፈጸመ በኋላም በዚህች ቀን በክብር ዐርፏል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ፍሥሐ ለኩሉ ዓለም ተወልደ ለነ ክርስቶስ"
(ቅዱስ ያሬድ)
እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዓለም ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ልደተ ክርስቶስ <3

ዓለማትን፣ ዘመናትን፣ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ፣ ወልደ አምላክ ነው። የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ሲሆን ራሱም እግዚአብሔር ነው። በባሕርየ ሥላሴ መበላለጥ የለምና ወልድ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው እንጂ አይበልጥምም አያንስምም።

እርሱ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ማዕከለ ዓለም ያለና ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ጌታ ነው። ቀዳማዊና ደኃራዊው አልፋና ኦሜጋ እርሱ ነው።
(ዮሐ. ፩፥፩ ፣ ራእይ ፩)
ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክ (ሮሜ. ፱፥፭)፣ የዘላለም አባት፣ የሰላምም አለቃ ነው።
(ኢሳ. ፱፥፮)
ቅድመ ዓለም ሲሠለስ ሲቀደስ ኑሮ ይህንን ዓለም ፈጠረ። እርሱ ሁሉን ያስገኛል እንጂ ለእርሱ አስገኝ የለውም።

አንድ ክርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ ሊያውቀው የሚገባ መሠረተ እምነት ይሔው ነው!

መድኃኒታችን ክርስቶስን በዚህ መንገድ የማያምንና የማያመልክ ሁሉ እርሱ ክርስቲያን አይደለም። ምንም ሥጋችንን ተዋሕዶ ብዙ የትሕትና ሥራዎችን ቢሠራም፣ ቢሰቀል፣ ቢሞትም እርሱ እግዚአብሔር ነውና ፍጹም አምላክ ፍጹምም ሰው ብለን ልናመልከው ይገባል።

እንደ አርዮስ፣ ንስጥሮስና ልዮን የማይገቡ ነገሮችን መናገር ጐዳናው የሞት መዳረሻውም ገሃነመ እሳት ነው። እንኳን የክብር ባለቤት መድኅን ክርስቶስ ላይ በፍጡር ላይ እንኳ የማይገባ ነገርን የተናገረ ሁሉ የገሃነም ፍርድ አለበት።

ለእርሱ የዓለም ፈጣሪ፣ ጌታና ቤዛ ለሆነው መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ምስጋና፣ ጌትነት፣ ውዳሴና አምልኮ ይሁን!

እግዚአብሔር አዳምን በሰባት ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በኋላ ግን ንስሐ ስለ ገባ "ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው።

ከዚህ በኋላ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር፣ ሱባኤ ይቆጠር፣ ምሳሌም ይመሰል ገባ።

ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ።
ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሳፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል።
ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት /ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል።

ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል። እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል።

<3 ልደተ ክርስቶስ እምድንግል <3

"ጊዜው ሲደርስ አንባ ይፈርስ።" እንዲሉ አበው መድኃኒታችን የጥልን ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ፣ ከኃጢአትና ከሞት ቁራኝነት ይፈታን ዘንድ፣ ለሰዎች ቤዛ ይሆን ዘንድ፣ ትንቢተ ነቢያትን ይፈጽም ዘንድ፣ በቀጠሮ (በአምስት ቀን ተኩል) ወደዚህ ዓለም መጣ።

የሰማይና የምድር ጌታ በእንግድነት በመጣ ጊዜም እርሱን ለመቀበል በተገባ የተገኘች ንጽሕት ሙሽራ ድንግል ማርያም ሆነች። ከእርሷ በቀር ለዚህ ክብር ሊበቃ የሚቻለው ፍጥረት እንኳን ኃጢአት ካደከመው የሰው ልጅ ከንጹሐን መላእክት ወገን አልተገኘም።

በጊዜውም መልአከ ትፍሥሕት ቅዱስ ገብርኤል መጋቢት ፳፱ ቀን ወደ ድንግል ወርዶ የአምላክን ሰው የመሆን ዜና ከውዳሴና ከክብር ጋር ነገራት።
(ሉቃ. ፩፥፳፮)
ድንግልም ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሰማይና ምድር የማይችሉትን መለኮትን ተሸከመች።

ልክ ሙሴ በደብረ ሲና እንዳያት ዕጽ ድንግል ማርያምንም ባሕርየ መለኮቱ አላቃጠላትም። ስለዚህም ነገር "ወላዲተ አምላክ፣ ታኦዶኮስ፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንግሥተ አርያም፣ የባሕርያችን መመኪያ....." እያልን እንጠራታለን።

ግሩም ድንቅ ጌታን ጸንሳ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን እስኪፈጸም ድረስ ብዙ ተአምራትን ሠራች። መላእክተ ብርሃን እየታጠቁ አገለገሏት፤ አመሰገኗት። ልጇን አምላክ፣ እርሷን እመ አምላክ እያሉ ተገዙላት።

ከዚያም በሮሙ ቄሣር በአውግስጦስ ዘመን ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዋጅ ወጥቷልና እመ ብርሃን ማርያም ከቅዱሳኑ ዘመዶቿ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ አባቷ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ሔደች።

በዚያም ሳሉ የምትወልድበት ጊዜ ቢደርስ በፍጹም ድንግልና እንደ ጸነሰችው ሁሉ በፍጹም ድንግልና ወለደችው።
(ኢሳ. ፯፥፲፬ ፣ ሕዝ. ፵፬፥፩)
ተፈትሖም አላገኛትም። ልማደ አንስትም አልጐበኛትም። ምጥም አልነበረባትም።

ድንግል ማርያም ክርስቶስን በወለደች ጊዜ ልጇ አምላክ፣ እርሷም የአምላክ እናት መሆኗ ይታወቅ ዘንድ፦
፩.የብርሃን ጐርፍ ፈሰሰ፤
፪.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ወርደው "ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም" እያሉ ዘመሩ፤
፫.ትጉሐን እረኞች በቅዱስ ገብርኤል መሪነት መጥተው ክብሩን ተካፈሉ፤
፬.በሰማይም ልዩ ኮከብ ድንግልና ልጇ ተስለውበት ዝቅ ብሎ ታየ፤
፭.ቅድስት ሰሎሜም በድፍረት የድንግልን ሆድ ዳስሳ እጇ ቢቃጠል እንደ ገና በተአምራት ድኖላታል።

በጊዜውም በምሥራቅ የፋርስ፣ የባቢሎንና የሳባ ነገሥት አስቀድሞ ከበለዓም በኋላም ከዠረደሸት በተረዱት መሠረት ኮከቡን በማየታቸው ታጥቀው ተነሱ።

ከምሥራቅ አፍሪቃና ከእስያም በተመሳሳይ ኮከቡን በማየታቸው አሥራ ሁለት ነገሥታት በየግላቸው አሥር፣ አሥር ሺህ ሠራዊትን እየያዙ ድንግልንና ንጉሥ ልጇን ፍለጋ ወጡ።

አሥራ ሁለቱ ነገሥታት ከነ ሠራዊታቸው ሲሔዱ ስንቃቸው በማለቁ ዘጠኙ ነገሥታት ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ። ሦስቱ ግን በፍጹም ጥብዓት ከሠላሳ ሺህ ሠራዊት ጋር በኮከብ እየተመሩ ኢየሩሳሌም ደረሱ።

እነዚህም መሊኩ የኢትዮጵያ (የሳባ ንጉሥ ተወላጅ)፣ በዲዳስፋና መኑሲያ (ማንቱሲማር) ደግሞ የፋርስና የባቢሎን ነገሥታት ናቸው። ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱም ሄሮድስና ሠራዊቱ ታወኩ።

እነርሱ ግን የቤተ ልሔምን ዜና ከጠየቁ በኋላ በጐል ድንግል ማርያምን፣ ክርስቶስን፣ ዮሴፍና ሰሎሜን አገኙ። ለሁለት ዓመታት እነርሱን ፍለጋ ደክመዋል ተንከራተዋልና ደስታቸው ወሰን አጣ።

በእመቤታችንና በልጇ ፊት በደስታ ዘለሉ። "አንፈርዓጹ ሰብአ ሰገል" እንዲል። ወርቁን፣ እጣኑንና ከርቤውንም ገብረው በግንባራቸው በፊቱ ሰገዱ። ሦስት ጊዜም እየወጡ እየገቡ ቢመለከቱት በኪነ ጥበቡ አንዴ እንደ ሕፃን፣ በሁለተኛው እንደ ወጣት፣ በሦስተኛው እንደ አረጋዊ ሆኖ ታይቷቸው ፈጽመው አድንቀዋል።

ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም "ወአስነቀቶሙ ሕብስተ ሰገም" እንዲል የገብስ ዳቦ ጋግራ ድንግል ለሰብአ ሰገል ሰጠቻቸው። እነርሱም ይህንን እየተመገቡ የሁለት ዓመቱን መንገድ በአርባ ቀን ሲጨርሱት ዳቦው ግን ያ ሁሉ ሺህ ሰው ተመግቦት አላለቀም። ተአምራትንም ሠርቷል።

የልደቱ ነገር እንዲሁ ተተርኮ የሚያልቅ አይደለምና ይቆየን። የከርሞ ሰውም ይበለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ አምላካችን አማኑኤል፣ ዕለተ ማርያም እና ዕለተ ጌና ስቡሕ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አማኑኤል <3

የክርስትና ሃይማኖት እጅግ ብዙ ምሥጢራትን ያካትታል። ታላቅ መዝገብ ነውና። ሰዎች እናልፋለን። ዓለምም ታረጃለች እንጂ ምሥጢረ ክርስትና አያረጅም። እዚህ ቦታ ላይ ይጠናቀቃልም አይባልም።

"አማኑኤል" የሚለውን ስም መረዳት የሚቻለው በአንድ መንገድ እርሱም ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን ጠንቅቆ በመማር ነው። ምሥጢራት ደግሞ በእምነት ለማይኖር በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም።

እግዚአብሔር አንድም ነው፤ ሦስትም ነው። ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነቱ፤ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው።

ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው። ዓለምን ከፈጠረ በኋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምህርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው።

ይኸውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው። ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርህ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ። እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ፦
ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው። ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ባለቤቱ ያውቃል።

እግዚአብሔር በኋለኛው ዘመን ሰው የሆነበት ምሥጢር እኛን ለማዳን ቢሆንም ይሔው ተግባሩ ዓለም ሳይፈጠር ያሰበው እንጂ በአዳም ውድቀት ምክንያት ድንገት የታሰበ አይደለም።

እግዚአብሔር አዳምን በሰባት ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በኋላ ግን ንስሐ ስለ ገባ "ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው።

ከዚህ በኋላ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር፣ ሱባኤ ይቆጠር፣ ምሳሌም ይመሰል ገባ።

ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ።
ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሳፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል።
ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት /ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል።

ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል። እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል። መድኅን ክርስቶስም ተወልዶ አድኗቸዋል።

"አማኑኤል" የሚለው ቃል ከዕብራይስጥ ልሳን (ከጽርዕ የሚሉም አሉ።) በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም "እግዚአብሔር ምስሌነ - እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ።" እንደ ማለት ነው።
(ኢሳ. ፯፥፲፬ ፣ ማቴ. ፩፥፳፪)
ምሥጢሩ ግን ከዚህ የሠፋ ነው።
"አማኑኤል" ማለት "እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋን ከነፍሳችን ነፍስን ነስቶ በፍጹም ተዋሕዶ እኛን መሰለን።" ማለት ነው። በሌላ አነጋገርም "አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ።" እንደ ማለት ነው።

ይህንን ሲያደንቁ ቅዱሳን ሊቃውንት "ወዝንቱ ስም ዓቢይ ወኢይደሉ ፈሊጦቶ - ይህ ስም ታላቅ ነው። ወደ ሁለት ሊከፍሉት (ሊለዩት) አይገባም።" ብለው ምሥጢረ ተዋሕዶን አስረድተዋል።
(ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ)

ስለዚህም ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ እኛን ያድን ዘንድ በተለየ አካሉና በከዊነ ቃልነቱ ፍጹም የድንግል ማርያምን ሥጋ ተዋሕዶ የሰውነትንም የአምላክነቱንም ሥራ ሠርቶ አድኖናል።

በማኅጸነ ድንግል ከተቀረጸባት ደቂቃ ጀምሮም ፍጹም ተዋሕዶን ፈጽሟልና መቼም መች አምላክም፣ ሰውም ነው እንጂ ወደ ሁለትነት ማለትም አምላክን ለብቻ ሰውን ለብቻ አናደርግም።

ስለዚህም ዛሬም ዘወትርም እግዚአብሔር ቃል የተዋሐደው ሥጋችን በዘባነ ኪሩብ ሲሠለስና ሲቀደስ ይኖራል። እርሱ ጌታችን እስከዚህ ድረስ ወዶናልና።

ፈጣሪያችን በሦስትነቱ ሥላሴ (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) በአንድነቱ እግዚአብሔር፣ ኤልሻዳይ፣ አልፋ፣ ወዖ፣ ቤጣ፣ የውጣ፣ ኦሜጋ..... እያልን እንደምንጠራው ሁሉ በሥጋዌው ምክንያት አማኑኤል፣ መድኃኔ ዓለም፣ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ እያልን እንጠራዋለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሰማዕቱ አባ አብሳዲ እና ለጻድቁ አባ በግዑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አባ አብሳዲ <3

ቅዱሱን የመሰሉ አባቶች "መስተጋድላን" ይባላሉ። ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው። መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው።

ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ። ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ። የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከሁለት አካላት ጋር ነው። በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖታችሁን ካዱ፤ ለጣዖትም ስገዱ።" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው።

በተለይ ሁለተኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል። የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ።

ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ። ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ። ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል።

ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል። ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው። ፍቅረ መስቀሉን የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም።

ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው። ጌታችን "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ።" (ማቴ. ፲፮፥፲፰) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን።

ቅዱስ አባ አብሳዲ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። እንደርሱ በቅድስና ያጌጠ ባልንጀራም ነበረው። ስሙም ቅዱስ አላኒቆስ ነበር።

እነዚህ ክርስቲያኖች በዚያ የመከራ ዘመን ግራ ቀኝ ሳይሉ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን ጠንቅቀው ተምረዋል። በጐውን ጐዳና አጽንተው በመገኘታቸውም መንፈስ ቅዱስ ሁለቱንም በአንዴ ለእረኝነት ጠራቸው።

ጵጵስና ከዚህ በፊት እንደ ተመለከትነው እዳ (ኃላፊነት) እንጂ ምድራዊ ክብርን ማጋበሻ መንገድ ወይም የሥጋ ድሎትን መፍጠሪያ ዙፋን አይደለም። ያም ሆኖ ምርጫው የመንፈስ ቅዱስ ሲሆን ደስ ያሰኛል።

በእርግጥም የክርስቶስን መንጋ እንደሚገባ መምራትና በለመለመው የወንጌል መስክ ማሰማራት የሚያስገኘው ክብር በሰማያት ታላቅ ነው። ያም ቢሆን ግን ከብዙ መከራ በኋላ እንጂ እንዲሁ በዋዛ አይደለም። የእግዚአብሔር ጸጋውና መንግሥቱ ያለ መከራ አትገኝምና።

ቅዱሳኑ አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስም ይህንን ኃላፊነት የተረዱ ነበርና ታጥቀው ሥራቸውን ጀመሩ። እንደ ሐዋርያት ሥርዓትም ያላመነውን ማሳመን፣ ያመነውን በሃይማኖቱ ማጽናት፣ የጸናውን ደግሞ ለምሥጢራተ ቅድሳት (ሥጋ ወደሙ) ማብቃት የዘወትር ተግባራቸው ነበር።

ቅዱሳኑ በዚህ ተጋድሏቸው ሳሉ ዜናቸው በየቦታው ተሰማ። ነገር ግን ይህ ዝናቸው የወለደው መከራን ነበር። በጊዜው አውሬው ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን ከዋሉበት አላሳድር ካደሩበትም አላውል ብሎ ነበር።

ለክፋቱ እንዲመቸው በየሃገሩ ጨካኝ መኮንኖችን ሾመ። በምድረ ግብጽም ሁለት ገዢዎችን ሲያኖር አንዱ አርያኖስ (በኋላ አምኖ ሰማዕት ሆኗል።) ሁለተኛው ደግሞ ሔርሜኔዎስ ይባላሉ።

እነዚህ መኳንንት ግብጽን ለሁለት ተካፍለው በሥራቸው ገዥዎችን ሹመው በግፍ ተግባራቸው ክርስቲያኖችን ይቀጡ ገቡ። የስቃይ ተራው ደግሞ የሁለቱ ቅዱሳን (አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስ) ነበርና ተከሰሱ።

ለፍርድ ይቀርቡ ዘንድም አርያኖስ በማዘዙ ወታደሮች መጡ። ነገሮችን አስቀድሞ የሚያውቀው ቅዱስ አብሳዲም ምንም ስለ ክርስቶስ ለመሞት ቢቸኩልም መንጋውን እንዲሁ ሊበትን ግን አልወደደም።

ስለዚህም ወታደሮችን "እባካችሁ ሕዝቡን ልሰናበት አንድ ቀን ታገሱኝ።" አላቸው። ወታደሮቹ ከፊቱ የሚታየው ግርማው ደንቋቸው ነበርና ፈቀዱለት። ቅዱሱም ከሕይወቱ የቀረችውን ሃያ አራት ሰዓት ይጠቀምባት ዘንድ ምዕመናን ልጆቹን ሁሉ ጠራ።

ቅዳሴ ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ፈትቶ ለሁሉም አቀበላቸው። (በጊዜው የማይቆርብ ክርስቲያን አልነበረምና።)

ከቅዳሴ መልስም የተፈጠረውን ሁሉ ነግሮ ወደ ክርስቶስ ሊሔድ እንደ ናፈቀ ነገራቸው። ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ሲረዱ ፈጽመው አዘኑ። እርሱም በቀናችው እምነት እስከ ሞት ድረስ እንዲጸኑ አስተምሯቸው ከባልንጀራው ቅዱስ አላኒቆስ ጋር በወታደሮች እጅ ወደቀ።

እነርሱም ቅዱሳኑን ወስደው በመኮንኑ አርያኖስ ፊት ለፍርድ አቀረቧቸው። አርያኖስም የአባ አብሳዲ የፊቱ ግርማ ቢስበው ላለመግደል ወስኖ ሊያባብለው ወሰነ። "አንተ ክቡር ሰው ነህና ለንጉሡ ታዘዝ፤ ለጣዖትም እጠን።" አለው።

ቅዱስ አብሳዲ ግን "ክብሬ ክርስቶስ ነውና ፈጣሪዬን በምንም ነገር አልለውጠውም።" ሲል እቅጩን ነገረው። እንደማያሳምነው ሲረዳም ከአባ አላኒቆስ ጋር ያሰቃዩአቸው ዘንድ አዘዘ።

በምስክርነት አደባባይም በመንኮራኩር (አካልን የሚበጣጥስ ተሽከርካሪ ብረት ነው።) አበራዩአቸው። እግዚአብሔር ግን አዳናቸው። እንደ ገና እሳት አስነድደው እዚያ ውስጥ ጨመሯቸው። እሳቱም ግን ሊበላቸው አልቻለም።

በመጨረሻም መኮንኑ አንገታቸው ይሰየፍ ዘንድ አዘዘ። ከመሰየፋቸው በፊትም ቅዱሳኑ ጸሎትን አደረሱ። አባ አብሳዲ ነጭ የቅዳሴ ልብሱን ለብሶ ወደ ሰይፍ ቀረበ። ወታደሮች ደግሞ ሁለቱን ቅዱሳን እንደታዘዙት ሰየፏቸው። በክብርም ዐረፉ።

<3 አባ በግዑ ጻድቅ <3

እኒህ አባት በመካከለኛው ዘመን የሃገራችን ታሪክ ሰፊ ቦታን ይዘው ይገኛሉ። ተጋድሏቸውን የፈጸሙት በደብረ ሐይቅ ነው። ጻድቁ ብዙ ጊዜ የኋለኛው ዘመን ሙሴ ጸሊም ይባላሉ። ብዙ የሕይወታቸው ጐዳና ተመሳሳይ ነው።

ልክ ቅዱስ ሙሴ ጸሊም ከኃጢአት ከሽፍትነት ሕይወት እንደ መጣው ሁሉ አባ በግዑም አስቸጋሪ ሰው እንደ ነበሩ ይነገርላቸዋል። ከዚያ የከፋ የኃጢአት ኑሮ እግዚአብሔር ሲጠራቸው ግን ክሳደ ልቡናቸውን አላደነደኑም። "እሺ" ብለው ንስሐ ገቡ እንጂ።

ከዚያም በደብረ ሐይቅ (ወሎ) በፍጹም ተጋድሎ ኑረዋል። ያዩ ሁሉም ፍጹም ያደንቁ ነበር። ስትበላ ስትጠጣ የኖረችውን ሰውነት ራሳቸውን ውኃ ለዘመናት በመከልከል ቀጥተዋታል። ስለዚህም "ውኃ የማይጠጣው አባት" ይባሉም ነበር። ጻድቁ ሲያርፉ ፈጣሪያቸው አክብሯቸዋል።

አምላከ አበው ቅዱሳን አሠረ ፍኖታቸውን ይግለጽልን። ከበረከታቸውም ያድለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት እና ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

እስኪ ዛሬ በጥቂቱ የተባረኩ (ቡሩካት) እናቶቻችን እንዘክር። "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል። እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቡርክት እምቡሩካን፣ ኅሪት እምኅሩያን" ናትና።

ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች። ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች። እርሷ እመ ብርሃን፣ የአምላክ እናቱ፣ የሰውነታችን መመኪያ ናትና።

እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት፣ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ" ማለታችን ነው።
፩."ንጽሕት" ትባላለች። ሌሎች ሰዎች (ቅዱሳን) ቢነጹ ከገቢር፣ ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም። እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከኃልዮ ንጽሕት ናት።
"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ።
(ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው፤ ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም።)" እንዲል።
(ተአምረ ማርያም)
፪."ጽንዕት" እንላታለን። ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው። እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና።
"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት።
(ቅዱስ ያሬድ)
ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም - ማርያም ዘላለማዊት ድንግል ናት።" እንዳለ።
(መጽሐፈ ቅዳሴ)
፫.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን። ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው። እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ - የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና።
፬.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን። ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል፣ እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና።

የእመ ብርሃን ይቆየንና ደግሞ ሌሎች ቅዱሳት እናቶቻችንን እንመልከት። እናቶቻችን ስናከብር የምንጀምረው በቅድስት ሔዋን ነው። ብዙ ጊዜ የእናታችን ሔዋን ጥፋቷ እንጂ በጐ ነገሯ፣ ደግነቷ፣ ንስሐዋ አይነገርላትም። ሆኖም እናታችን ቅድስት ሔዋን ክብር የሚገባት ሴት ናት።
ክርስቶስ ሰው የሆነ እርሷንና ልጆቿን ለመቀደስ ነውና። "ከመ ይስዓር መርገማ ለሔዋን ዲበ ዕፅ ተሰቅለ" እንዲል።
(ድጓ)

ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን እነ ሐይከል፣ እድና፣ ሣራ፣ ርብቃ፣ አስኔት፣ ሲፓራ፣ ሐና፣ ቤርሳቤህን የመሰሉ እናቶቻችን በበጐው መንገድ ፈጣሪን ደስ አሰኝተዋል። በዘመነ ሥጋዌም ቅዱሳቱ ሐና፣ ኤልሳቤጥ፣ ማርያም፣ ሶፍያ፣ ሰሎሜ፣ ዮሐና እና ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በጐነታቸው ያበራል።

ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለሁለት ሺህ ዓመታት የተነሱ አእላፍ ቅዱሳት እናቶቻችንን ግን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም። በቅድስናቸው አራዊትን ያሰገዱ፣ ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ፣ አጋንንትን የረገጡ፣ በዘንዶ ላይ የተጫሙ ብዙ እናቶችን ቤተ ክርስቲያን አፍርታለች።

ዛሬም ቢሆን በበርሃና በከተማ በጐውን ጐዳና የተከተሉ ብዙ እናቶች እንዳሉን እናውቃለን። አንድም እናምናለን። ግን በከተሞች የምንመለከተው ሥርዓቱን የለቀቀው የበርካታ እኅቶቻችን አካሔድ ለሃገርም ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ ስጋት ነው። ክብርና ነውር የማይለይበት ዘመን ይመስላል።

ይህንን እያነበባችሁ ያላችሁ እኅቶቼ! አንድ ነገር ልንገራችሁ። በመልካቸው ብዙዎችን ያጋጩ፣ አጊጠው በመታየታቸው ብዙዎችን ያሰናከሉ፣ ለብዙ ምዕመናንም የጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሴቶች በታሪክ ነበሩ።

የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ያሉት ከመሬት በታች ነው። አፈር በልቷቸዋል። ስም አጠራራቸውም ጠፍቷል። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ዛሬ በዘላለማዊው እሳት እየተቃጠሉ በሲኦል በጥልቁ ውስጥ አሉ።

እናም ወገኖቼ! ይህን አውቀን እንንቃ። ይህ ዓለም ጠፊም አጥፊም ነውና። እድሜአችን ቢረዝምና ከዚህ በኋላ ለመቶ ዓመታት ብንኖርም እርሱም ማለቁ አይቀርምና። ምርጫችን ዘላለማዊው ሕይወት ይሁን ትላለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአምስቱ ቅዱሳን መቃብያን እና ቅዱስ ዮሐንስ ከማ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አምስቱ መቃብያን <3

እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው። አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ነቢይና ካህን አድርጐ ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው።

አባታችን አዳም ግን ስህተት አግኝቶት ከገነት ወጣ። መከራና ፍዳም አገኘው። በኋላም ለመቶ ዓመታት አልቅሶ ንስሐ ገባ። ጌታም ንስሐውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው።

ስለዚህም ምክንያት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ትንቢት ሲነገር፣ ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር፣ ምሳሌም ሲመሰል ኖረ። ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ።

ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ። በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም። ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ።

ከእርሱም ይስሐቅ ከዚያም ያዕቆብ ደጋጉ ተገኙ። ያዕቆብም "እስራኤል" ተብሎ በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ። በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ረሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው።

በዚያም ለሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ። እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እስራኤልን አሰባቸው። የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው።

ይኸውም በጸናች እጅ በበረታችም ክንድ፣ በዘጠኝ መቅሰፍት፣ በአሥረኛ ሞተ በኩር፣ በአሥራ አንደኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው። በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው። ከዚህ ዘመን ጀምሮም እስራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ።

አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና አሮን በክህነት መሯቸው። ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ በአሮን አልዓዛር ተተኩ።

ከዚህ በኋላ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል መሳፍንት እየተቀያየሩ አስተዳደሯቸው። ሲበድሉ ጠላት እየገዛቸው ሲጸጸቱ በጐ መስፍን እየመጣላቸው ከነቢዩ ሳሙኤል ደረሱ።

በዚህ ጊዜም ሕዝቡ እንደ አሕዛብ ሥርዓት ንጉሥ በመፈለጋቸው ክፉው ሳዖል ለአርባ ዓመት ገዛቸው። ቀጥሎ ግን እንደ አምላክ ልብ የሆነ ቅዱስ ሰው ዳዊት ነግሦላቸው እስራኤል ከፍ ከፍ አሉ። ከቅዱስ ዳዊት እስከ ሮብዓም ቆይተው ግን እስራኤል ከሁለት ተከፈሉ።

አሥሩ ነገድ በሰማርያ ሲኖሩ ግፍን ስላበዙ ስልምናሶር ማርኮ አሦር አወረዳቸው። ባሮችም አደረጋቸው። ሁለቱ ነገድ ደግሞ ከብረው ገነው በኢየሩሳሌም ቢኖሩም እነርሱም አመጸኞች ነበሩና ናቡከደነጾር ወስዶ የባቢሎን ባሪያ አደረጋቸው።

እግዚአብሔር ግን እንደ ነቢያቱ ቃል ሰባው ዘመን ሲፈጸም በኃይል ወደ ርስታቸው መለሳቸው። በዚያም ዘሩባቤል የሚባል ደግ ንጉሥ ነግሦላቸው ቤተ መቅደስ ታንጾላቸው ኖሩ። ክፋታቸው ግን ማብቂያ አልነበረውምና ከዘሩባቤል በኋላ ቅን ንጉሥን ማግኘት አልቻሉም።

እግዚአብሔር ግን ምሕረቱንና መግቦቱን አይተውምና አልዓዛርን የመሰሉ ደጋግ ካህናትን እያስነሳ ሰው እስከሚሆንባት ቀን ድረስ አቆይቷቸዋል። በዚህም ምክንያት ይህ ዘመን "ዘመነ ካህናት" ተብሏል።

በዚህ በዘመነ ካህናት ውስጥ ደግሞ በጐነታቸው የታወቀላቸው ግን ደግሞ መከራው የበዛባቸው እስራኤላውያን ነበሩ። ብዙ ጊዜ የሚጠሩት "መቃብያን" በሚል ስም ነው።

በያዕቆብ እስራኤል፣ በዔቦር ዕብራውያን፣ በይሁዳ አይሁድ፣ በፋሬስ ፈሪሳውያን፣ በሳዶቅ ሰዱቃውያን እንደተባሉት ሁሉ እነዚህም በአባታቸው በመቃቢስ ምክንያት መቃብያን ተብለዋል። ታሪካቸው ሰፊና በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈ ሲሆን እኛ ግን በአጭሩ አንዷን የታሪክ ዘለላ ብቻ እንመለከታለን።

በዘመኑ መቃቢስ የሚባል ደግ ሰው አምስት ወንዶች ልጆችን (መቃብያንን) ወልዶ ነበር። እነዚህም በመልክ ይህ ቀራችሁ የማይባሉ በጠባይ እጅግ የተመሰገኑ በኃይላቸው ጽናትም የተፈሩ ነበሩ።

በተለይ ሦስቱ ከግሩማን አራዊት አንበሳና ድብ ታግለው ያሸነፉ በጦርነትም ጠላትን ያንበረከኩ ነበሩ። ታዲያ ይህ ሁሉ የተሰጣቸው ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና ፈጣሪያቸውን በንጹሕ ልብ ያመልኩት ነበር።

በዘመኑ ደግሞ ሞዐባውያንና ሜዶናውያን አካባቢውን ያስገብሩ ነበር። በተለይ የሞዐቡ ንጉሥ ጺሩጻይዳን ከክፋቱ ብዛት ሰባ ጣዖታት በወንድና በሴት ምሳሌ አስቀርጾ ያመልክ ነበር። ከዚያም አልፎ ሕዝቡን "አምልኩ" እያለ ያውክ፣ ይቀጣ፣ ይገድልም ነበር።

ቅዱሳን መቃብያን ይህንን ሲሰሙ ወደ እርሱ ገሰገሱ። ምንም እንኳ ሊያጠፉት ኃይል ቢኖራቸውም አላደረጉትም። ይልቁኑ ቀርበው ዘለፉት እንጂ።

እርሱም "ጣዖትን አናመልክም።" ስላሉ ለአንበሳ ጣላቸው። አንበሶቹም ለቅዱሳኑ ሰግደው የንጉሡን ወታደሮች ፈጇቸው። እርሱም ሦስቱን ወደ እሥር ቤት ጣላቸው። በዚህ ጊዜ ሁለቱ ወንድሞቻቸው መጥተው ተቀላቀሉ።

ቀጥሎም አምስቱንም አስወጥቶ በሰይፍ አስመታቸው። ከተገደሉ በኋላም ወደ ውኃ ጥሏቸው በእሳት አቃጥሏቸው ነበር። ባይሳካለት ስለ ተቆጣ ሳይቀበሩ እንዲጣሉ አዘዘ። ከአሥራ አራት ቀናት በኋላም የቅዱሳኑ አካል እንደ መብረቅ እያብለጨለጨ ተገኝቶ በክብር እንዲቀበር ሆኗል።

ቀሪው ታሪካቸው በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈ አይደለምን!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ <3

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ "አርእስተ ሊቃውንት" ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው። አባቱ ኤስድሮስ (ባስልዮስ የሚሉም አሉ።) እናቱ ደግሞ ኤሚሊያ ይባላሉ። ባል እና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው አምስት ወንድና አንዲት ሴት ልጅን አፍርተዋል። የሚገርመው ሴቷ (ቅድስት ማቅሪና) ገዳማዊት ስትሆን አምስቱም ወንዶች ጳጳሳት መሆናቸው ነው።

የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው። አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት አንዱ ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው። ነገር ግን ቅርብ ጊዜ ከድረ ገጾች (websites) እየገለበጡ የሚጽፉ አንዳንድ ወንድሞች ይህንን የሚያፋልስ ነገር ጽፈው ተመልክተናል።

ቅዱስ ባስልዮስ ገዳማዊ ጻድቅ፣ ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ፣ የብዙ ምዕመናን አባት፣ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት፣ ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት (ከፍጹምነት) የደረሰ አባት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያስገነባ እርሱ ነው።

እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት። መጽሐፈ ቅዳሴውንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው። ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል። ታዲያ ይህ ሊቅ፣ ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል።

በዘመኑ እዚያው ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ (በዘመኑ አጠራር ባሪያ) ነበር። የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው። ለሥራ ሲገባ የሰውየውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት። ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ። ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ።

እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል። ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስህተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስህተትን ጨመረ። ወደ ጠንቅዋይ (መተተኛ) ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ። መተተኛው ግን "ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ።" አለው።

ያ ከንቱ ሰው "እሺ" አለ። መተተኛው ቀጠለ "በል! ሌሊት ስድስት ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ። ከዚያ ይመጣልሃል።" ብሎ ላከው። አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ ነጥቆ ወደ ጥልቁ የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው።

ጋኔኑ ሰውየውን አለው፦ "አንተ የፈለከው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ። በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ።" አለው። ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ። ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው።

በማግስቱ ጧት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ። አንዲት ልጃቸው "ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ።" አለች። ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም። ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ።

እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ። ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተውት አልወደዱምና ጾሙ፣ ጸለዩ፣ ተማለሉ። በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ። ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት።

አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ "ቤተ ክርስቲያን ተሳልመህ፣ ቆርበህ፣ ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ፣ አማትበህስ ታውቃለህ?" አለችው። እርሱም "በጭራሽ አላውቅም።" አላት። "ለምን" ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት። በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት።

ለረዥም ሰዓት አለቀሰች። ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት። ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ። ወዲያው ግን በሕሊናዋ አንድ ሐሳብ መጣላት። "ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል።" አለች። ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች።

እርሱም "ልጄ ሆይ! አይዞሽ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው። ሒጂና ባልሽን አምጪው።" አላት። ሒዳ አመጣችው። ቅዱሱም ያን ሰው "መዳን ትፈልጋለህ?" አለው። ሰውየው መልሶ "ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር።" አለው። ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን "ሒጂና ጸልይ ከአርባ ቀን በኋላ ትመጫለሽ።" ብሎ አሰናበታት።

በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በአራት አቅጣጫ በመስቀል አተመው። ትንሽ ምግብ ሰጥቶት "ከሦስት ቀን በኋላ እመጣለሁ።" ብሎት ሔደ። ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር። በሦስተኛው ቀን መጥቶ "እንዴት ነህ?" አለው። "አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ።" አለው። "አይዞህ!" ብሎት ወጣ።

በስድስተኛው ቀን መጥቶ "አሁንስ?" አለው። "አባ! ስቃዩ ቀረልኝ። ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል።" አለው። "በርታ" ብሎት ሔደ። በዘጠነኛው ቀን ተመልሶ "ደግሞ አሁንሳ?" አለው። "አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው።" አለው።

እንዲህ በሦስት በሦስት ቀናት እየተመላለሰ ለአሥራ ሦስት ጊዜ ጠየቀው። በሠላሳ ዘጠነኛው ቀን መጥቶ "ዛሬ ምን አየህ?" ቢለው "አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ።" አለው። ቅዱስ ባስልዮስ በአርባኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት፣ ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ያን ሰው ከመሃል አቁሞ "እግዚኦ በሉ።" አላቸው።

ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ። ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች። በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ። ቅዱሱ በጸሎቱ ለአርባ ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ።

የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና። በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው። ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው። ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር ፮ ቀን ዐርፏል።

አምላከ ቅዱስ ባስልዮስ እኛንም ከኃጢአት ማሠሪያ ፈትቶ ከአጋንንት ሴራ ይሰውረን። ከሊቁም በረከትን ያሳትፈን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ክቡሩ አባት ሆይ! ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብን ግለጽልኝ። ይልቁንም የጸሎትህ ኃይለ ቃል ረዳቴ በመሆን ዓሥራት በኩራት አድርጎ ይጠብቀኝ።"
(መልክአ ገብረ መንፈስ ቅዱስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ማቴዎስ ነዳይ እና ቅዱስ አውስግንዮስ አረጋዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አባ ማቴዎስ <3

ቅዱሱ አባት በቤተ ክርስቲያናችን ስመ ጥር ነው። በተለይ ትርጓሜ ወንጌል ላይ እንደ አብነት ሲጠቀስ የተአምረ ማርያምን ሥርዓት በማዘጋጀቱ የበዓላት መቅድመ ተአምር ላይ ስሙ አለ። ቅዱሱ ለእመቤታችን በነበረው ፍቅር ድንግል ብዙ ጊዜ ትገለጥለት ነበርና።

ቅዱስ ማቴዎስ ግብጻዊ አባት ሲሆን የነበረው በመካከለኛው ዘመን ውስጥ (ማለትም በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ነው። በቤቱም መልካም ወላጆችና ያዕቆብ የሚባል ወንድምም ነበረው።

እንዲያውም አንዴ እናቱ ቅዱሱን ጸንሳ ሳለች የበቁ አበው ሆዷን እጅ ነስተው "ቅዱስ ፍሬ በማኅጸንሽ ውስጥ አለ።" እንዳሏት ይነገራል። ቅዱስ ማቴዎስ በልጅነቱ ወደ እግዚአብሔር ከመገስገስ ቅዱስ ቃሉን ከመማር በዘለለ ሌላ ሃሳብ አልነበረበትም።

ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ተከታትለው በማረፋቸው ከወንድሙ ያዕቆብ ጋር ለብቻቸው ቀሩ። ብዙ የወላጆቹ ሃብት ቢኖርም ቅዱስ ማቴዎስ ስለ መካፈል አላሰበም። ከለበሳት ጨርቅ በቀር ምንም ሳይዝ ወደ በርሃ ገሰገሰ።

ሊመነኩስ ወዶ የደብረ ቅዱስ አቡፋናን አበው ቢጠይቃቸው "አይሆንም" አሉት። ምክንያቱም በጊዜው ወንድሙን ያውቁት ስለ ነበር እየመጣ እንዳያውካቸው "አስፈቅድ" ማለታቸው ነበር። ቅዱስ ማቴዎስ ግን ወደ ሌላ ገዳም ሔዶ አለቀሰ።

አባቶችም ወደ ወንድሙ ሔደው ስለ ማለዱት ፈቀደለት። ስለዚህም በደብረ አቡፋና መነኮሰ። ትንሽ ቆይቶ ግን ወንድሙ ያዕቆብ "ለወንድሜ ያልሆነች ዓለም ለእኔም አትረባኝም።" ብሎ በርሃ ገብቶ በቅቶ ዐርፏል።

ቅዱስ ማቴዎስም በገዳሙ በፍቅርና በመታዘዝ ሲያገለግል ዜና ትጋቱ ተሰማ። ይህንን ከሰሙት ጳጳሳት አንዱ አባ ጴጥሮስ ያለ ፈቃዱ ከገዳም አስወጥቶ በመንበረ ጵጵስናው ረዳት አደረገው። እርሱ ግን አንገቱን አቀርቅሮ ተጋድሎውን በጾምና በጸሎት ቀጠለ።

ነገር ግን ሰይጣን በሴቶች አድሮ ፈተነው። በጣም አዝኖ ጳጳሱን "አሰናብተኝ" አለው። "እንቢ" ቢለው የክብር ልብሱን (የጳጳሱን) አውጥቶ በመቀስ ብጥስጥስ አደረገውና በጳጳሱ ፊት አኖረለት።

ፈጽሞ የተበሳጨው ጳጳሱም በየቀኑ ሦስት መቶ እንዲሰግድ ወደ ቤት እንዳይጠለልና ሌሎች ቀኖናዎችን ቅጣት ሰጥቶ ወደ በርሃ አሳደደው። ቅዱስ ማቴዎስም መሻቱ ይህችው ነበረችና ደስ እያለው ሔደ።

ለሁለት ዓመታትም የቀኑ ሐሩር የሌሊቱ ቁር እየተፈራረቀበት ቅጣቱን በመፈጸሙ የፍትሐት ደብዳቤ ተላከለት። አንድ ቀን ግን በገዳሙ የነበረ አንድ የበቃ አባት ክብረ ማቴዎስ ተገልጦለት "የብዙዎች አባት ትሆናለህ።" አለው።

ውዳሴ ከንቱን ፈጽሞ የሚጠላት ቅዱሱ ግን አዘነ። ሰዎች እያከበሩት ስለተቸገረም ገዳሙን ለቀቀ። በሔደበት ገዳምም ድንቅ ነገሮቹን እያዩ ሲያከብሩት በአንድ ገዳም የማይቀመጥ ሆነ። ከአንዱ ወደ ሌላውም ይሔድ ነበረ።

ቅዱስ ማቴዎስ ከጳጳሱ ዘንድ እያለ ቅስናን ሹሞት ነበርና በገዳማት ይቀድሳል። ከብቃቱም የተነሳ በቅዳሴ ሰዓት ማኅበረ መላእክትን ያያቸው ነበር። መድኃኒታችን ክርስቶስም ሕፃን መስሎ ከፊቱ ይቀመጥ ነበር። ስለዚህ ነገርም ዕንባው እንደ ዥረት ውኃ ይፈስ ነበር። እየቀደሰም ተመስጦ (ተደሞ) ይመጣበት ነበር።

ዘወትር የፈጣሪውን ጌትነት እያደነቀ ይመራመር ነበርና አንዴ ቀና ቢል ሰባቱ ሰማያት ተከፈቱለት። እግዚአብሔርንም ከጽርሐ አርያም (ሰባተኛው ሰማይ) ከፍ ብሎ አየው። ደንግጦ ዝቅ ቢል ደግሞ ከጥልቁ በታች ተመለከተው።

በዚህ ጊዜ "ይህን ያሳየኸኝ ጌታዬ እኔ ማነኝ!" ሲል አለቀሰ። ሁሌ ዓርብም ሕማማተ ክርስቶስን በተለይ መድኃኒታችን መቸንከሩን እያሰበ ረጅም ችንካርን በጉልበቱ ውስጥ ይከት ነበር። ለቀናት ስለማያወጣውም ደሙ ፈሶ አካሉ መልኩ ይቀይር ነበር።

እንዲህ ካሉ የቅድስናና የተጋድሎ ዓመታት በኋላም ሌላ ጥሪ ከፈጣሪው መጣለት። አበው በጸሎት ላይ ሳለ መጥተው አሠሩት። "ምን አደረኳችሁ አባቶቼ?" ቢላቸው "ከዚህ በኋላ የግብጽ ፓትርያርክ ነህ።" አሉት። ቢለምናቸውም እንቢ አሉት።

"እንግዲያውስ" ብሎ ምላሱን አውጥቶ በመቀስ ቆርጦ ጣላት። መናገር የማይችል ሰው ክህነት አይሾምምና። (እንዲህ ነበር አበው ሥልጣንን የሚሸሿት) ነገር ግን እመቤታችን ከሰማይ ወርዳ "ወዳጄ! ነገሩ የልጄ ፈቃድ ስለ ሆነ እሺ በላቸው።" ብላ አዲስ ምላስን ሰጠችው።

የግብጽ ሰማንያ ሰባተኛ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ሥርዓተ ሲመቱ ሲፈጸም የወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ራሱ በዚያ ነበረችና ክንፍ አውጥታ በራ ቅዱስ ማቴዎስን ስትስመው ሁሉም አዩ። ከሰማይም ማኅበረ መላእክት "አክዮስ - ይገባዋል" ብለው ሲጮሁ ተሰማ።

ቅዱስ ማቴዎስ ምንም ፓትርያርክ ቢሆንም ለትምህርት፣ ለቅዳሴና መሰል ነገሮች ካልሆነ ከበዓቱ አይወጣም ነበር። ገንዘብ የሌለው ጥሩ ልብስ የማይለብስ ነበርና "ነዳዩ" እየተባለ እስካሁን ይጠራል።

በዘመነ ጵጵስናው ብዙ ተግባራትን ሲከውን ዋኖቹ ግን የእመቤታችን ተአምር በሥርዓት እንዲነበብ ማድረጉ ቀድሞ ይጠቀሳል። በተረፈም የጌታችን ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣም ትልቅ አስተዋጽኦን አድርጓል።

በተሰጠው የትንቢት ሃብትም ወደ ፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን ተመልክቷል። የተናገራቸውም ሁሉ ተፈጽመዋል። በመጨረሻው ግን ያሰቃየው የነበረው የወቅቱ የግብጽ ከሊፋ (ክፉ ሰው) አስጠርቶ አካሉ እስኪደቅ ድረስ ገረፈው።

ቅዱስ ማቴዎስም ወደ እመቤታችን ጮኸ። ድንግልም ወርዳ አጽናናችውና "አሳርፍሃለሁ" አለችው። ሕዝቡን ተሰናብቶም በዚህች ቀን ዐርፏል።

<3 ቅዱስ አውስግንዮስ አረጋዊ <3

ይህ ቅዱስ አባት በሃይማኖቱ ጽናት፣ በምግባሩ ብዛት ለወጣቶች አብነት መሆን የቻለ አባት ነው። በብዛት የሚታወቀው በሰማዕትነቱ ቢሆንም በቅዱስ ሰውነቱ በርካታ መልካም ነገሮችን ሠርቷል።

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መነሻ አካባቢ (ዘመነ ሰማዕታት ሊጠናቀቅ ሲል ማለት ነው።) የቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (የንጉሡ) ወታደር ሁኖ ተቀጠረ። ንጉሡ ወደ መክስምያኖስ ለጦርነት ሲሔድ በሰማይ ላይ መስቀልና "ኒኮስጣጣን" የሚል ጽሑፍን ተመልክቷል።

ሁሉም ሰው ለመተርጐም ሲፈራ ወጣቱ አውስግንዮስ ግን በድፍረት ለንጉሡ ክብረ መስቀልንና ትርጉሙን አስረዳ። በቅዱሱ ንጉሥ ሥርም በወታደርነት ለሃያ ዓመታት አገለገለ።

ከዚያም ሥጋዊ ተግባሩን ትቶ በጾምና በጸሎት፣ ሰዎችንም በማስታረቅ፣ በማስተማርም ተወሰነ። ፈጣሪ ጸጋውን አብዝቶለትም ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ደረሰ።

በጊዜውም የነበረው ከሃዲው ዑልያኖስ "ሰዎችን አስታርቀሃልና ክርስቶስን አምልከሃል።" በሚል በዚህች ቀን አንገቱን አሰይፎታል። ዑልያኖስን ደግሞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተበቅሎታል።

አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል ይማረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ ሐዋርያ ወልደ ነጐድጓድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ <3

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግሥተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነው። ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ በገሊላ አካባቢ አድጐ ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል።
(ዮሐ. ፩፥፴፱)

ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር። ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕፃን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው። ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል።
(ዮሐ. ፲፱፥፳፭)

ከእርሷ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ። ስንኳን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላእክትም ማዕረጉ ከፍ አለ። ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል። ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል። ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ በታናሽ እስያ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መስበኩ ይታሰባል። ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ለሰባ ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው። ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል።

ሦስት መልእክታት፣ ራእዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል። ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል። ከእሳት እስከ ስለት እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል። እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጓቸዋል።

<3 ቅዱሱ በኤፌሶን <3
ይህች ኤፌሶን የሚሏት ሃገር መገኛዋ በቀድሞው ታናሽ እስያ (አሁን ቱርክ አካባቢ) ሲሆን ብዙ ሐዋርያት አስተምረውባታል። ያም ሆኖ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ያመጣች አልነበረችምና ቅዱስ ዮሐንስ ሊሔድ ተነሳ።

ከደቀ መዛሙርቱ መካከልም ቅዱስ አብሮኮሮስን (ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ነው።) አስከትሎ እየጸለዩ በመርከብ ላይ ተሳፈሩ። ሐዋርያት አበው መከረኞች ናቸውና ማዕበል ተነሳባቸው። በጥቂት አፍታም መርከባቸው በማዕበሉ ተበታተነች።

ቅዱስ አብሮኮሮስ በስባሪ ላይ ተሳፍሮ ወደ አንዲት ደሴት ደረሰ። ግን ከንጹሑ መምህሩ ቅዱስ ዮሐንስ ተለይቷልና አለቀሰ። ፍቁረ እግዚእ ግን ያለ ምግብና ውኃ ማዕበለ ባሕር እያማታው ለአርባ ቀናት ቆየ።

እርሱ በፈጣሪው ፍቅር የተመሰጠ ነበርና አለመመገቡ አልጐዳውም። በአርባኛው ቀን ግን ደቀ መዝሙሩ ወዳለበት ደሴት ማዕበሉ አደረሰው። ሁለቱ ቅዱሳን ተፈላልገው ተገናኙ። እጅግም ደስ ብሏቸው ፈጣሪን አመሰገኑ።

አምላካቸው ወደዚህች ደሴት ያመጣቸው በጥበቡ ነውና ሲዘዋወሩ ሁለት ነገርን አስተዋሉ።
፩ኛ.የደሴቷ ሁሉም ነዋሪ የሚያመልኩት ጣዖትን ነው።
፪ኛ.አብዛኞቹ ልዑላን (የቤተ መንግሥት ውላጆች) ናቸው። ሮምና የሚሏት አንዲት ሴት ደግሞ እነዚህን ሁሉ እየመገበች ታስተዳድራለች።

ቅዱሳኑ በቦታው በቀጥታ ትምህርተ ወንጌልን ቢናገሩ እንደ ማይቀበሏቸው ስለ ተረዱ ሌላ ፈሊጥን አሰቡ። እንዳሰቡትም ወደ እመቤት ሮምና ቤት ሒደው በባርነት ተቀጠሩ።

ለእርሷም "ድሮ የአባትሽ ባሮች የነበርን ሰዎች ነን።" ስላሏት ሁለቱን ቅዱሳን እሳት አንዳጅና ገንዳ አጣቢ አደረገቻቸው። ለሰማይ ለምድሩ የከበዱ እነዚህ ቅዱሳን የካዱትን ይመልሱ ዘንድ በባርነት ግፍን ተቀበሉ። የመከር (የማሳመኛ) ጊዜ ሲደርስም አንዳች አጋጣሚ ተፈጠረ።

ቅዱሳኑ ዮሐንስና አብሮኮሮስ ወደ መታጠቢያ ቤቱ ሲገቡ ሰይጣን በውስጥ ኖሮ ደንግጧልና እወጣለሁ ብሎ ሲሮጥ የንጉሡን ልጅ ረግጦ ገደለው። ሮምናና የአካባቢው ሰዎች ከበው ሲላቀሱ ቅዱሳኑ ቀረቡ።

ሮምና ግን በቁጣ "ልትሣለቁ ነው የመጣችሁ?" በሚል ቅዱስ ዮሐንስን በጥፊ መታችው። መላእክት እንኳ ቀና ብለው ሊያዩት የሚከብዳቸው ሐዋርያ ይህንን ታገሰ። በጥፊ ወደ መታችው ሴት ቀረብ ብሎም "አትዘኝ! ልጁ ይነሳል።" አላትና ጸለየ።

ወደ ሞተውም ቀረብ ብሎ በጌታችን ስም አስነሳው። በዚህ ጊዜም ሮምናን ጨምሮ በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ለቅዱስ ዮሐንስ ሰገዱ። እርሱ ግን ሁሉንም አስነስቶ ትምሕርተ ሃይማኖትን፣ ፍቅረ ክርስቶስን ሰበከላቸው።

በስመ ሥላሴ አጥምቆ ካህናትን ሹሞ ቤተ ክርስቲያንም አንጾላቸው ወጥቷል። በኋላም ለሮምናና ለደሴቷ ሰዎች ክታብ (መልእክትን) ጽፎላቸዋል። ይህች መልእክት ዛሬ ሁለተኛዋ የዮሐንስ መልእክት ተብላ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትታወቃለች።

ቅዱስ ዮሐንስ ቀጥሎ የተጓዘው ወደ ኤፌሶን ነው። በዚህች ከተማ የምትመለክ አርጤምስ (አርጢሞስ) የሚሏት ጣዖት ነበረች። አርጤምስ ማለት መልክ የነበራት ትዕቢተኛ ሴት ስትሆን አስማተኛ ባሏ ነው እንድትመለክ ያደረጋት።

ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ ምዕመናን ከእርሷ እንዲርቁ ማድረግ ችሏል። ጨርሶ ያጠፋት ግን ቅዱስ ዮሐንስ ነው። በቦታውም ብዙ ግፍ ደርሶበት በርካታ ተአምራትን አድርጓል። ቤተ ጣዖቱንም በተአምራት አፍርሶታል።

<3 የፍቅር ሐዋርያ <3
ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን "የፍቅር ሐዋርያ" ትለዋለች። ለሰባ ዘመናት በቆየ ስብከቱ ስለ ፍቅር ብዙ አስተምሯል። ፍቅርንም በተግባር አስተምሯል። በየደቂቃውም "ደቂቅየ ተፋቀሩ በበይናቲክሙ - ልጆቼ ሆይ! እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።" እያለ ይሰብክ ነበር።

በተለይ ደግሞ ከፈጣሪው ክርስቶስ ጋር የነበረው ፍቅር ፍጹም የተለየ ነበር። በዚህ ምክንያትም ጌታ ባረገ ጊዜ እንዲህ ብሎታል፦ "ለፍጡር ከሚገለጥ ምሥጢር ከአንተ የምሠውረው የለኝም።"

ቀጥሎም በንጹሕ አፉ ስሞታል።
ሊቁ፦
"ሰላም ለአፉከ ለዮሐንስ ዘሰዓሞ
ንጽሐ ኅሊናሁ ወልቡ ለዐይነ ፍትወትከ ሶበ አደሞ።" እንዳለው።
(መልክአ ኢየሱስ)

ቅዱስ ዮሐንስ ከእመቤታችንም ጋር ልዩ ፍቅር ነበረው። እርሷ እንደ ልጇ ስትወደው እርሱ ደግሞ እንደ እናቱ ልቡ እስኪነድ ድረስ ይወዳት ነበር። እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ ተከትሎ ያገኛት እመቤቱ ናትና።

ከዚያ ሁሉ ጸጋና ማዕረግ የመድረሱ ምሥጢርም ድንግል ናት። ለአሥራ አምስት ዓመታት በጽላሎተ ረድኤቷ (በረዳትነቷ ጥላ) ተደግፎ አብሯት ሲኖር ብዙ ተምሯል። ከመላእክትም በላይ ከብሯል። ከንጽሕናዋ በረከትም ተካፍሏል።

ስለ ድንግል ማርያምም "ነገረ ማርያም" የሚል ድርሰት ሲኖረው "የሰኔ ጐልጐታንም" የጻፈው እርሱ ነው።

ድንግል ባረፈችበት ቀንም ልክ እንደ ልጇ ክርስቶስ እርሷም ስማው ታቅፋው ዐርፋለች። ሊቃውንቱ ለዚህ አይደል በንጹሕ ከንፈሮቿ መሳምን (መባረክን) ሲሹ፦
"በከመ ሰዓምኪ ርዕሰ ዮሐንስ ቀዳሚ
ስዒሞትየ ማርያም ድግሚ።" ያሉት።

ታላቁ ቅዱስ ሐዋርያ ዕድሜው ዘጠና ዓመት በሆነው ጊዜ ተሰውሯል። ከዚያ አስቀድሞም የዓለምን ፍጻሜ ተመልክቷል። ዛሬ ያለበትን የሚያውቅ ቸር ፈጣሪው ነው።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሕፃናተ ቤተ ልሔም እና አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሕፃናተ ቤተ ልሔም <3

በሮሙ ቄሣር በአውግስጦስ ዘመን ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዋጅ ወጥቷልና እመ ብርሃን ማርያም ከቅዱሳኑ ዘመዶቿ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ አባቷ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ሔደች።

በዚያም ሳሉ የምትወልድበት ጊዜ ቢደርስ በፍጹም ድንግልና እንደ ጸነሰችው ሁሉ በፍጹም ድንግልና ወለደችው።
(ኢሳ. ፯፥፲፬ ፣ ሕዝ. ፵፬፥፩)
ተፈትሖም አላገኛትም። ልማደ አንስትም አልጐበኛትም። ምጥም አልነበረባትም።

በጊዜውም በምሥራቅ የፋርስ፣ የባቢሎንና የሳባ ነገሥት አስቀድሞ ከበለዓም በኋላም ከዠረደሸት በተረዱት መሠረት ኮከቡን በማየታቸው ታጥቀው ተነሱ።

ከምሥራቅ አፍሪቃና ከእስያም በተመሳሳይ ኮከቡን በማየታቸው አሥራ ሁለት ነገሥታት በየግላቸው አሥር አሥር ሺህ ሠራዊትን እየያዙ ድንግልንና ንጉሥ ልጇን ፍለጋ ወጡ።

አሥራ ሁለቱ ነገሥታት ከነ ሠራዊታቸው ሲሔዱ ስንቃቸው በማለቁ ዘጠኝ ነገሥታት ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ። ሦስቱ ግን በፍጹም ጥብዓት ከሠላሳ ሺህ ሠራዊት ጋር በኮከብ እየተመሩ ኢየሩሳሌም ደረሱ።

እነዚህም መሊኩ የኢትዮጵያ (የሳባ ንጉሥ ተወራጅ)፣ በዲዳስፋና መኑሲያ (ማንቱሲማር) ደግሞ የፋርስና የባቢሎን ነገሥታት ናቸው። ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱም ሄሮድስና ሠራዊቱ ታወኩ።

እነርሱ ግን የቤተ ልሔምን ዜና ከጠየቁ በኋላ በጐል ድንግል ማርያምን፣ ክርስቶስን፣ ዮሴፍና ሰሎሜን አገኙ። ለሁለት ዓመታት እነርሱን ፍለጋ ደክመዋል ተንከራተዋልና ደስታቸው ወሰን አጣ።

በእመቤታችንና በልጇ ፊት በደስታ ዘለሉ። "አንፈርዓጹ ሰብአ ሰገል" እንዲል። ወርቁን፣ እጣኑንና ከርቤውንም ገብረው በግንባራቸው በፊቱ ሰገዱ። ሦስት ጊዜ እየወጡ እየገቡ ቢመለከቱት በኪነ ጥበቡ አንዴ እንደ ሕፃን፣ በሁለተኛው እንደ ወጣት፣ በሦስተኛው እንደ አረጋዊ ሆኖ ታይቷቸው ፈጽመው አድንቀዋል።

ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም "ወአስነቀቶሙ ሕብስተ ሰገም" እንዲል የገብስ ዳቦ ጋግራ ድንግል ሰጠቻቸው። እነርሱም ይህንን እየተመገቡ የሁለት ዓመቱን መንገድ በአርባ ቀን ሲጨርሱት ዳቦው ግን ያ ሁሉ ሺህ ሰው ተመግቦት አላለቀም። ተአምራትንም ሠርቷል።

ሰብአ ሰገል ቅዱስ መልአክ እንደ ነገራቸው በሄሮድስ ዘንድ ሳይሆን በሌላ ጐዳና ተጉዘው ሃገራቸው መግባታቸውን ንጉሡ ሰማ። እንደ ዘበቱበት ሲያውቅም የሚያደርገው ጠፍቶበት ወደ ቤቱ ገባ።

በሕሊናው የሚመላለሰውም አንድ ነገር ብቻ ነበር። የአይሁድ ንጉሥ የተባለውን (እርሱስ የሰማይና የምድር ሁሉ ንጉሥ ነው።) እንዴት ሊያጠፋው እንደሚችል ያስብ ነበር። በዚያች ሰዓትም ሰይጣን በሰው ተመስሎ ወደ እርሱ ቀረበ።

ሕፃኑን እንዴት ሊገድለው እንደሚችል ነግሮት በዓለም ታይቶ የማይታወቀውን ጭካኔ አስተማረው። ርጉም ሄሮድስም ሠራዊቱን ጠርቶ "አዋጅ ንገሩልኝ።" አላቸው።

እነርሱም "በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ በይሁዳም የምትገኙ እናቶች፦ አውግስጦስ ቄሣር ሕፃናትን በማርና በወተት አሳድገህ ለሹመት አብቃልኝ። ለእናቶቻቸውም ወርቅና ብር ስጥልኝ ስላለ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸውን ሕፃናት ሁሉ አምጡ።" እያሉ አዋጁን ነገሩ።

የቤተ ልሔምና የአካባቢዋ እናቶችም ያላቸው አንድም ሁለትም እየያዙ የሌላቸው ደግሞ እየተዋሱ ወደ ሄሮድስ ዘንድ ይዘዋቸው መጡ። ያን ጊዜ አውሬው ሄሮድስ እናቶችን በአንድ ቦታ እንዲታጐሩ አድርጐ ሕፃናቱን በወታደሮቹ አሳፍሶ ወደ ተራራ አወጣቸው።

በሥፍራውም ተወዳዳሪ በሌለው ጭካኔ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ወታደሮቹን አሰልፎ ሕፃናቱን አሳረዳቸው። ሰይፍ የበላቸው የቤተ ልሔም ሕፃናት ቁጥርም መቶ አርባ አራት ሺህ ሆነ።

የሕፃናቱ ደም ከተራራው እንደ ጐርፍ ወረደ። የእናቶች የጡት ወተትም በመሬት ላይ ይፈስ ነበርና ተቀላቀለ። የቤተ ልሔም እናቶች አንጀታቸው በእጥፉ ተቆረጠ። ታላቅ ሰቆቃም አካቢውን ሞላው፤ ዋይታም ሆነ።

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ እንዳለው ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ። "ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች። የሉምና መጽናናት አልቻለችም።"
(ማቴ. ፪፥፲፰ ፣ ኤር. ፴፩፥፲፭)

ሰይጣን ግን አላማው እንዳልተሳካና ድንግልና አምላክ ልጇ መሸሻቸውን ሲያውቅ ይህንኑ ለሄሮድስ ሹክ አለው። ስለዚህም ንግሥተ አርያም ድንግል ማርያምና ወልደ አምላክ ልጇ በስደት ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ተንገላቱ።

እንደ ገናም ክፉ ሰዎች መጥተው ለሄሮድስ "አንተ የምትሻው በዘካርያስ ቤት አለና ግደለው።" አሉት።
ሄሮድስም ወታደሮቹን ልኮ ሕፃኑን ቅዱስ ዮሐንስን ቢያጣው ደጉን ነቢይ አረጋዊ ዘካርያስን በቤተ መቅደስ መካከል ገድሎታል።

በጊዜው የሚፈርድ እግዚአብሔርም ስለ ሕፃናቱ ደም ተበቅሎ ሄሮድስን አጠፋው። ወደ እመቀ እመቃትም አወረደው። መቶ አርባ አራት ሺህው ንጹሐን ሕፃናት ግን ሥልጣነ ሰማይ ተሰጣቸው። ከእነርሱ በቀር ማንም በማያውቀው ምሥጢርና ዜማ ፈጣሪያቸውን ይሠልሱትና ይቀድሱት ዘንድም አደላቸው።
(ራእ. ፲፬፥፩)

አባ ሕርያቆስ በሐዳፌ ነፍስ ድርሰቱ "ያስምዓነ ቃለ መሰናቁት ዘሕፃናት - የሕፃናትን የመሰንቆ ድምጽ ያሰማን።" እንዳለ።
(ቅዳሴ ማርያም)

እነዚህ መቶ አርባ አራት ሺህ ንጹሐን ሕፃናት ዛሬ በሰማይ ለምዕመናን ምሕረትን ለጨካኞች ፍርድን ይለምናሉ። በፍርድ ቀንም በጌታ ፊት በክብር ቅንዋቶቹን ይዘው ይመጣሉ።

ክብራቸው ታላቅ ነውና ለቅዱሳን ሕፃናት ምስጋና ይሁን!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ቴዎናስ ሊቀ ጳጳሳት <3

ይህ ቅዱስ ሰው ተወልዶ ያደገው በእስክንድርያ (ግብጽ) ሲሆን ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። እርሱ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን ተምሮ ጸጋው ቢበዛለት ከምዕመንነት ወደ ዲቁና፣ ከዲቁና ወደ ቅስና ማዕርግ ተሸጋገረ።

ቀጥሎም ለታላቅ ኃላፊነት ተመረጠ። አባ መክሲሞስ ባረፈ ጊዜ የግብጽ አሥራ ስድስተኛ ፓትርያርክ ሆነ። ግን ኃላፊነቱ ሠርግና ምላሽ (የተመቸ) አልነበረም። ምክንያቱም እርሱ ሊቀ ጳጳሳት ሲሆን ዘመነ ሰማዕታት በመጀመሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፤ ተጨፈጨፉ።

አብያተ ክርስቲያናትም ተቃጥለው አለቁ። በዚሀ ጊዜ ቅዱስ ቴዎናስ እየዞረ ሕዝቡን ያጸና ነበር። በተለይም የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን አንጾ ለሕዝቡ ያቆርብ፣ ያስተምር ነበር።

በዘመነ ሲመቱ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስን ጨምሮ ብዙ አርድእትን አፍርቷል። ሥልጣነ እግዚአብሔር ጋርዶት ስለ ነበር አገልግሎቱን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል።

የጻድቅ ሰው አቤል አምላከ የውሃቱን ይስጠን። የዋሃንን ያብዛልን። ከበረከቱም ይክፈለን።

ጥር ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፪.ቅዱስ ቴዎናስ ሊቀ ጳጳሳት
፫.ቅዱስ አላኒቆስ ሰማዕት
፬.ቅድስት ሳቤላ ነቢዪት
፭.ቅዳሴ ቤታ ለድንግል (በደብረ አባ ሲኖዳ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
፭.ሊቁ አባ ሕርያቆስ
፮.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ

"እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።
.....አቤል ከቃየን ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት። ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል።"
(ዕብ ፲፩፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ሰማዕታተ አክሚም <3

በቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን ታሪክ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከተካሔደባቸው አካባቢዎች አንዷ ሃገረ አክሚም ናት። አክሚም ማለት የቀድሞ የግብጽ አውራጃ ናት። በተለይ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በርካታ ክርስቲያኖች በፍቅር ይኖሩባት ነበር።

በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ጥቡዓን፣ ታማኞች፣ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉና ዘወትር ቅዱስ ቃሉን ለመስማት የሚተጉ ነበሩ። ለዚህም ደግሞ ከሊቀ ጳጳሱ አባ ብኑድያስ ጀምሮ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ፣ ንፍቅ ዲያቆናቱ፣ መጋቢዎቹ፣ አናጉንስጢሶቹ (አንባቢዎቹ)፣ መምህራኑ፣ መሳፍንቱም ሳይቀር ለክርስቶስ ፍቅር የተጉ መሆናቸው አስተዋጽኦ ነበረው።

በተለይ ግን ሁለት ወንድማማቾች የነበራቸው ቅድስና ብዙዎችን ስቧል። እኒህ ቅዱሳን ዲዮስቆሮስና ሰከላብዮስ ይባላሉ። ከባለ ጸጋና ባለ ሥልጣን ቤተሰብ ቢወለዱም ክርስትናቸው አልቀዘቀዘም። የወጣትነት ስሜት ሳያሸንፋቸውም ወደ በርሃ ተጓዙ።

በዚያም በቅድስና ኑረው ለክህነት ማዕረግ በቅተዋል። ቅዱሳኑ በገዳም ሳሉም መድኃኒታችን ክርስቶስ ተገልጦ "ወደ ትውልድ ሃገራችሁ አክሚም ተመለሱ። ክብረ ሰማዕታት ይጠብቃችኋል።" አላቸው። እነርሱም ደስ እያላቸው በፍጥነት ወደ አክሚም ወጡ።

በዚያ ሰሞን የጌና ጾም ተፈጽሞ የአክሚም ክርስቲያኖች ለበዓለ ልደት ዝግጅት ሲያደርጉ በጠላት ሠራዊት ተከበቡ። ይህ ሠራዊት የተላከው ከርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ሲሆን መሪው ደግሞ አርያኖስ ነው።

ዋናው ተልዕኮው ክርስቲያኖችን ለጣዖት ማሰገድ እንቢ ካሉ ደግሞ መግደል ነው። ክርስቲያኖቹ መከበባቸውን እያወቁ አልፈሩም። ታኅሣሥ ፳፱ ቀንም ሁሉም የከተማዋ ክርስቲያኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰበሰቡ።

በዚያም ሊቀ ጳጳሱ ሥርዓተ ቅዳሴን አደረሱ። ሁሉም በተመስጦ ይጸልዩ ነበርና የክብር ባለቤት ክርስቶስ በገሃድ ተገለጠላቸው። በዓይናቸው እያዩም ሥጋ ወደሙን አቀበላቸው። ቅዳሴው ሲጠናቀቅ ግን አርያኖስና ሠራዊቱ ደርሰው ሁሉንም ክርስቲያኖች ያዟቸው።

ክርስቶስን ክደው ከመገደል እንዲድኑ ተጠየቁ። እነርሱ ግን በአንድ ድምጽ "አይሆንም!" አሉ። በዚያን ጊዜ ወታደሮቹ በክርስቲያኖች አንገት ላይ በሰይፍ ይጫወቱ ያዙ።

በተራ አሰልፈው ጳጳሱን፣ ካህናቱን፣ ዲያቆናቱን፣ አንባቢዎችን፣ መሳፍንቱን ሳይጨምር ከአሥራ ስድስት ሺህ በላይ ክርስቲያኖች ደማቸው ፈሰሰ። የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ሞልቶ ደም ወደ ውጭ ሃያ ክንድ ያህል ፈሰሰ። በክርስቲያኖች ላይ ግፍ ተፈጸመ። አካባቢውም ያለ ወሬ ነጋሪ ቀረ። ግድያው ለሦስት ቀናት ቀጥሎ ጥር ፩ ቀን ቅዱሳን ዲዮስቆሮስና ሰከላብዮስ ሲገደሉ ተጠናቀቀ።

አምላከ ሰማዕታት ፍቅረ ሃይማኖታቸውን ያሳድርብን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ጥር ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት (ሊቀ ዲያቆናት)
፪.ቅዱሳን ሰማዕታተ አክሚም
፫.ቅዱሳን ዲዮስቆሮስ ወሰከላብዮስ
፬.ቅዱስ ለውንድዮስ ሰማዕት
፭.አባ መቃርስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
፭.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት

"እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።
.....አንዳንዶቹ ተነስተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር። ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም። በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሱ።
.....በሸንጐም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት።"
(ሐዋ ፮፥፰-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አባ ዮሐንስ ብፁዕ <3

ይህም ቅዱስ በተመሳሳይ የዘመነ ጻድቃን ቅዱሳን ፍሬ ነው። "ኢትርአይ ገጻ ወኢትስማዕ ድምጻ" በሚለው ሕገ ተባሕትዎ ለአርባ ዓመታት ተወስኖ ኑሯል።

ይህም ማለት አንድ ወንድ ከመነነ በኋላ ሴቶችን እንዲያይና ከእነርሱም ጋር እንዲያወራ አይፈቀድለትም። ሴትም ብትመንን ሕጉ ያው ነው። (ዛሬ እየተደረገ ያለውን ግን ፈጣሪ ይመርምረው።)

አባ ዮሐንስ ብፁዕም እንዲህ ባለ ፈሊጥ ማለትም በጾምና በጸሎት ከዓለም ተለይቶ፣ ከሴት ርቆ፣ ንጽሕናውን ጠብቆ ሲኖር አረጀ። በጊዜው በከተማ የሚኖር አንድ መስፍን ወዳጅ ነበረው። ይህ መስፍን ዘወትር ወደ ጻድቁ እየመጣ ይባረካል።

ሚስቱ ግን በረከቱን ሽታ ልታየው ብትሞክርም አልተሳካም። ሕገ ምናኔ አይፈቅድምና። በዚህ ነገር ፈጽማ ማዘኗን በጸጋ ያወቀው አባ ዮሐንስ ግን በራእይ ወደ እርሷ መጣ።

"ሚ ሊተ ወለኪ ብእሲቶ - አንቺ ሆይ! ለምን ካላየሁህ እያልሽ ትዘበዝቢኛለሽ? እኔ ነቢይ ወይ ጻድቅ አይደለሁ።" ብሏት ባርኳት ተሠወራት። እርሷም ደስ ብሏት ለባሏ ነገረችው። ባሏ ወደ ጻድቁ ሲሔድም ገና ሳይነጋገሩ አባ ዮሐንስ ሳቅ ብሎ "ሚስትህ ደስ አላት አይደል?" ብሎታል። ጻድቁ በዘጠና ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፎ ተቀብሯል።

አምላከ ጻድቃን ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን ይፈጽምልን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ታኅሣሥ ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ዮሐንስ አበ ምኔት
፪.አባ ዘካርያስ ገዳማዊ
፫.አባ ዮሐንስ ብፁዕ
፬.መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናት (ሄሮድስ የገደላቸው)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፫.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፭.አባ ሣሉሲ ክቡር ጻድቅ

"ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኑራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። እንደሚታዘዙ ልጆች ባለ ማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን 'እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።' ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።"
(፩ጴጥ ፩፥፲፫-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ኦ ማርያም! በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ።
እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን።
ወስቴ ሕይወት ዘበአማን።"

"ማርያም (እመቤታችን) ሆይ! ስለዚህ ነገር እንወድሻለን። ከፍ ከፍ እናደርግሻለን። የጽድቅ መብልን የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና።"
(አባ ሕርያቆስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ላል ይበላ ንጉሥ <3

በአሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ፦
በብሥራተ መልአክ ተወልዷል፤
ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል፤
የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት አድጓል፤
በወንድሙ ቢገረፍም ቂም አልነበረውም፤
ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል።

በዙፋን ላይ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም እርሱስ አኗኗሩ ገዳማዊ ነበር።

ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር። ለዛውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት (ጠርዝ) ብቻ ነበር።

በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል። በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን (ላስታን) ገንብቷል። ዛሬም ድረስ ምሥጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቃድስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው።

ሥራውን ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ አርፏል። ጌታችን ስምህን ያከበረ፣ ዝክርህን የዘከረ፣ ከቤትህ ያደረውን፣ ከርስተ መንግሥተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል። ይህቺ ዕለት ቅዱሱ ንጉሥ የተወለደባት ናት።

እኛን ስለ ወደደ ሰው የሆነ ጌታ ፍቅሩን ይሳልብን። ከድንግል እናቱና ከልደቱ በረከትም ያሣትፈን።

ታኅሣሥ ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ልደተ ክርስቶስ ስቡሕ
፪.ታኦዶኮስ (ድንግል ማርያም)
፫.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ (ልደቱ)
፬.ቅዱስ ላሊበላ (ልደቱ)
፭.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (ልደታቸው)
፮.ጻድቅ አቃርዮስ (ንጉሠ ሮሃ)
፯.ቅዱስ ቆሪል ገመላዊ
፰.ሰብአ ሰገል
፱.ዮሴፍና ሰሎሜ
፲.ቅዱሳን ሰማዕታተ አክሚም

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፪.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፫.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊት
፬.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ
፭.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።"
(ሉቃ ፪፥፲-፲፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ዕለተ ጌና <3

ከሳምንታት በፊት ጀምረን የክርስቶስን የማዳን ሥራ ለመገንዘብ እየሞከርን ቆይተናል። በተለይ ታኅሣሥ ፯ ቀን "ስብከት" በሚል ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን ትንቢት መነገሩን፣ ምሳሌ መመሰሉን፣ ሱባኤ መቆጠሩን ተመልክተን ነበር።

ቀጥለን ደግሞ ታኅሣሥ ፲፬ ቀን "ብርሃን" በሚል አምላካችን እንደ ምን ባለ ጥበቡ ብርሃኑን እንደ ሰጠን አንድም ወደን ወደ ጨለማ በገባን ጊዜ ሥጋችንን ተዋሕዶ ብርሃን እንደ ሆነልን ለማየት ሞክረናል።

ታኅሣሥ ፳፩ ቀን ደግሞ በበደላችን ምክንያት የነፍሳችንን እረኛ አጥተን ነበር። ለእኛው በደል እርሱ ክሶ ድጋሜ መልካም እረኛችን ሆኖ በሥጋ ማርያም መገለጡን አየን። የዛሬው በዓል ዕለተ ጌና ደግሞ ማሠሪያው ነው።

"ጌና" ማለት በቁሙ "ዕለተ ልደት ስቡሕ ማለትም አምላክ ሰው የሆነበት ምስጉን ቀን" እንደ ማለት ነው። ይህ ቀን ሁሌም በየዓመቱ "አማኑኤል (ጌና)" እየተባለ ይከበራል። ምክንያቱ ደግሞ ጌታ የተጸነሰ መጋቢት ፳፱ ቀን በመሆኑና ከዚህ ቀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ብንጨምር ይህ ዕለት ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ይመጣል።

ነገር ግን በአራተኛው ዓመት ዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜን ስድስት ስትሆን ዘጠኝ ወር ከስድስት ቀን ስለሚሆን ቀኑን እንዳይለቅ በዘመነ ዮሐንስ ዕለተ ልደቱ ለክርስቶስ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ይከበራል። ያም ሆኖ በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ ፳፰ን አክብረናል ብለን ፳፱ን አንተወውም። እርሱም ይከበራል።

በዚያው ልክ ደግሞ በሦስቱ አዝማናት (በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ) ልደቱ ታኅሣሥ ፳፱ ነው ብለን ፳፰ን አንሽረውም። "ጌና - አማኑኤል - ዕለተ ማርያም" እያልን እናከብረዋለን እንጂ። ብዙ ጊዜም በተለምዶ በዓለ ልደትን "ጌና" በማለት ፈንታ "ገና" የምንል ብዙዎች አለን።

ግን አበው ባቆዩልን ትውፊት "ጌና" ልደቱን የሚመለከት ሲሆን "ገና" ግን ባሕላዊ ጨዋታውን የሚመለከት ቃል ነው።

<3 ዕለተ ማርያም <3

ዳግመኛ ይህ ቀን ዕለተ ማርያም ይባላል። "ማርያም" የሚለው ቃል ብዙ ትርጉምን ያዘለ የእናታችንና የእመቤታችን፣ የተስፋችንና መመኪያችን የድንግል እመ ብርሃን ስም ነው።

ክርስቶስ ተጸነሰ፣ ተወለደ ስንል ለዚህ ሁሉ ምሥጢር ማካተቻና የድኅነታችን መጀመሪያ፣ የመመኪያችን ዘውድና የንጽሕናችን መሠረት ድንግል ማርያም ናትና ከፈጣሪ ቀጥሎ ታላቅ ክብር፣ ምስጋና፣ ስግደትና ውዳሴ ለእርሷ ይገባታል። መድኅናችን ክርስቶስ ያዳነን በእርሷ ምክንያት ነውና።

ሠለስቱ ምዕት (ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት) ይህንን ምሥጢር ሲያደንቁ እንዲህ ብለዋል፦
በሥጋ ማርያም ጌታ ተጸነሰ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ተወለደ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ አደገ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ተጠመቀ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ አስተማረ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ተሰቀለ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ሞተ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ተነሳ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ዐረገ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ዳግመኛ በሕያዋንና ሙታን ላይ ይፈርድ ዘንድ ከመለኮቱ ኃይል ጋር ይመጣል።
(መጽሐፈ ቅዳሴ)

ለድንግል ማርያም ክብርና ውዳሴ ከስግደት ጋር ይሁን!

የድንግል ማርያም ልጅ አማኑኤል ክርስቶስ በርኅራኄው ይማረን። ከበረከተ ልደቱም ያሳትፈን።

ታኅሣሥ ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.አማኑኤል አምላካችን
፪.በዓለ ጌና ስቡሕ
፫.ዕለተ ማርያም ድንግል
፬.መቶ ሰባ አራት ሰማዕታት (የቅዱስ ጳውሎስ ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱሳን (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፪.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፫.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
፭.ቅዱስ አባዲርና ቅድስት ኢራኢ

"የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርስዋ የተጸነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች። እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ 'እነሆ ድንግል ትጸንሳለች። ልጅም ትወልዳለች። ስሙንም አማኑኤል ይሉታል።' የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።"
(ማቴ ፩፥፳-፳፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ታኅሣሥ ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አብሳዲ ሰማዕት
፪.አባ አላኒቆስ ሰማዕት
፫.አባ በግዑ ጻድቅ
፬.አባ ፊልጶስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
፪.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
፫.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፮.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል። ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ።' ይላቸዋል። እላችኋለሁ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።"
(ሉቃ ፲፭፥፫-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅድስት አንስጣስያ <3

ይህች ቅድስት እንደ በርካቶቹ ቅዱሳት እናቶቻችን ሁሉ የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ናት። በቀደመችው ታናሽ እስያ አካባቢ ተወልዳ የነገሥታት ዘር በመሆኗ ያደገችው በቤተ መንግሥት ነው። አባቷ ከክቡራኑ አንዱ ቢሆንም ሙያው ጣዖትን ማምለክ ነበር።

ጊዜው የመከራ በመሆኑ ብዙ ሴቶች የሚኖሩት ክርስትናቸውን ደብቀው ነው። ከእነዚህ መካከል አንዷ ደግሞ የቅድስት አንስጣስያ እናት ናት። ማንን እንደምታመልክ አረሚ ባሏ አያውቅም ነበር።

አንስጣስያን በወለደች ጊዜም በድብቅ አስጠመቀቻት። ከሕፃንነቷ ጀምሮም ፍቅረ ክርስትና እንዲያድርባት ነገረ ሃይማኖትን አስተማረቻት። ቅድስት አንስጣስያ ወጣት በሆነች ጊዜ ግን ከውበቷ የተነሳ ተመልካቿ በዛ። እርሷ ግን ይህ ሁሉ የዓለም ኮተት አይገባትም ነበር።

በፈጣሪዋ ፍቅር ከመጠመዷ የተነሳ ለመሰል ነገሮች ትኩረት አልነበራትም። ትጾማለች፣ ትጸልያለች፣ ነዳያንና እሥረኞችን ትጐበኛለች። በዚህም ዘወትር ደስ ይላት ነበር። ነገር ግን አባቷ ባላሰበችው ጊዜ ለአንድ አረማዊ አጋባት። በጣም አዘነች ግን ተስፋ አልቆረጠችምና መፍትሔ ፈለገች።

ድንግልናዋን እንዳያረክስ በጫጉላዋ ቀን ታመምኩ ብላ ተኛች። ከዚያ በኋላም አንዴ በልማደ አንስት አንዴ በሕመም እያመካኘች አላስቀርብ አለችው። እርሱ የጦር አለቃ በመሆኑ ወደ ጦርነት ሲሔድ እርሷ ታጥቃ ስለ ቀናች እምነት የታሠሩ ክርስቲያኖችን ታገለግል ነበር።

ቁስላቸውን እያጠበች አንጀታቸውን በምግብ እየደገፈች ደስ ታሰኛቸውም ነበር። ባሏ ሲመለስ ግን ይህንን በመስማቱ ድጋሚ እንዳትወጣ ቆልፎባት ወደ ጦርነት ተመለሰ። ፈጽማ ስላዘነችበትም እግዚአብሔር በጠላቶቹ እጅ አሳልፎ ሰጠውና ሞተ።

እርሷም ከነ ድንግልናዋ ቀሪ ሕይወቷን ስትመራ መከራው ወደ እርሷ ደረሰ። ተይዛ ቀርባ በአረማውያን እጅ ብዙ ተሰቃየች። በዚህች ቀንም ስለ ክርስቶስ ተገድላ ክብረ ሰማዕታትን ተቀዳጀች።

<3 ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ <3

ቅዱሱ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የክርስቶስን ሕማማት ለመሳተፍ ሲተጉ ከኖሩ ጻድቃን አንዱ ነው። መሉ ጊዜውን በበርሃ ሲያሳልፍ ብዙ ተጋድሎን ፈጽሟል። በተለይ ሲጸልይ እግሩን ከዛፍ ላይ አስሮ ቁልቁል ከባሕር ውስጥ ሰጥሞ ነው። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ዕረፍቱን ታስባለች።

አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን ክብሩን ያድለን። ከወዳጆቹ በረከትም አይለየን።

ታኅሣሥ ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት
፪.ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ
፫.ቅድስት ዮልያና ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።"
(፩ጴጥ ፫፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አባ ዮሐንስ ከማ <3

ቅዱስ ዮሐንስ ከማ በዘመነ ጻድቃን (በተለይም በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ከተነሱ አበው አንዱ ነው። ቅዱሱ ድንቅ ሕይወት ስለ ነበረው በዜና አበው በስፋት ተጠቅሷል። መጽሐፈ ስንክሳር "ከማ" የሚለውን ቃል "ከማ ብሒል ካም - 'ከማ' ማለት 'ካም' ማለት ነው" ይላል።

"ካም" የሚለው ቃል ደግሞ ብዙ ጊዜ መልካቸው ጠቆር ላሉ ሰዎች የሚሰጥ ስም ነው። ምናልባት የድሮ የኢትዮጵያ ግዛት በነበረው ደቡብ ግብጽ የነበረ አባት እንደ መሆኑ የዘር ሐረጉ ከኢትዮጵያ የተመዘዘ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

ቅዱሱ በስፋት የሚታወቀው በድንግልና ሕይወቱ ነው። መልካም ቤተሰቦቹ በሥርዓት አሳድገው "እንዳርህ" አሉት። እንቢ ቢላቸው ብቸኛ ልጃቸው ነውና ፈጽሞ ሊያዝኑበት ነው። ደስታውን ለቤተሰቦቹ ሰውቶ በተክሊል ተዳረ።

እርሱ የሚሻው በድንግልና መኖርን ነውና ጥበበኛ እግዚአብሔር ሚስቱ የተቀደሰች እንድትሆን አደረጋት። በሠርጋቸው ምሽት ቅዱስ ዮሐንስ ከማ መልከ መልካሟን ሙሽራ በድንግልና ይኖሩ ዘንድ ቢጠይቃት በደስታ አነባች።

ምክንያቱም እርሷም ያገባችው ቤተሰብን ለማስደሰት እንጂ ፈቃዷ በድንግልና መኖር ነበርና። ሁለቱም ስላደረገላቸው ፈጣሪን እያከበሩ የድንግልና ሕይወት ተጋድሎን ቀጠሉ። ቅዱሳኑ በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ አንዲት ምንጣፍን እያነጠፉ አንድ ልብስንም በጋራ ለብሰው እያደሩ ድንግልናቸውን ጠበቁ።

አምላከ ድሜጥሮስም ቅዱስ መልአኩን ልኮላቸው በመካከላቸው ያድር ክንፉንም ያለብሳቸው ነበር። ክብራቸውን ይገልጥ ዘንድም በቤታቸው መካከል ታላቅ ዛፍን ያለ ማንም ተካይነት አበቀለ።

በዚህ ጊዜ ግን ቅዱስ ዮሐንስ ከማ ድንግሊቱን ሚስቱን "የከተማ ኑሮ ይብቃን፤ ወደ በርሃ እንሒድ።" አላት። እርሷም "ፈቃድህ ፈቃዴ ነው።" ስላለችው እርሷን ወደ ደናግል ገዳም አስገብቶ እርሱ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ተጓዘ።

ቅድስቲቱ አስቀድማ ጸጋው በዝቶላት ነበርና ድውያንን ትፈውስ ነበር። የገዳሙ እመ ምኔት ሆና መርታ በክብር አረፈች። ቅዱስ ዮሐንስ ከማም በቅዱስ መልአክ መሪነት መጀመሪያ ወደ አባ ዳሩዲ ሔዶ መነኮሰ።

በመጨረሻም በቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ገዳም ጐን ማደሪያን አነጸ። በዚያም በመቶ የሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርትን አፍርቶ በአበ ምኔትነት አገለገለ። ለእመቤታችንና ለቅዱስ አትናቴዎስ ልዩ ፍቅር የነበረው ቅዱሱ ከበርካታ የቅድስና ዘመናት በኋላ በዚህች ቀን በክብር ዐርፎ ተቀብሯል።

አምላከ ቅዱሳን ይራዳን፣ ይባርከን፣ ይቀድሰን። ከወዳጆቹ በረከትም ያሳትፈን።

ታኅሣሥ ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን አምስቱ መቃብያን
፪.ቅዱስ ዮሐንስ ከማ እና የተቀደሰች ሚስቱ
፫.ቅዱስ ዳንኤል መነኮስ
፬.ቅዱስ ኒቆላዎስ መኮንን

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፮.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
፯.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ

"ቃሌን የሚጠብቅ በትእዛዜም ጸንቶ የሚኖር በረከቴን የሚያገኝ በእኔ ዘንድ የሚከብር እርሱ ነው።
ቃሌን የሚጠብቅ በትእዛዜም ጸንቶ የሚኖር ሰው ሁሉ ከምድር የተገኘውን ድልብ ይበላል። ቅን ልቡና ያላቸው ደጋጎች ነገሥታት ወደ ገቡበት ወደ ገነትም ገብቶ ይኖራል።"
(፩መቃ ፲፪፥፵፫-፵፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ሰላም ለልደትከ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያ
ለሰብአ ግብጽ ወኢትዮጵያ
ሞገሰ ልደትከ አባ በአዕይንትያ ርእያ
ነፍስየ ትባርኮሙ ወታስተብፅዎሙ ነያ
ለጸጋ ዘአብ ወእግዚእ ኀረያ"

(ለኢትዮጵያና ለግብጽ ሰዎች ሐዋርያ የሆንክ ተክለ ሃይማኖት ለልደትህ ሰላምታ ይገባል።
የልደትህን ክብር በዓይኖቿ ዓይታ ሰውነቴ አባትህ ጸጋ ዘአብንና እናትህ እግዚእ ኀረያን እነሆ ታመሰግናቸዋለች፤ ከፍ ከፍም ታደርጋቸዋለች።)
(ነግሥ)

Читать полностью…
Subscribe to a channel