gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ዕረፍተ ድንግል <3

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር። ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር።

ዓለም ተፈጥሮ አዳምና ሔዋን ስተው መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው በኀዘን ንስሐ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት) በኋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ።" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው።

ከአዳም አንስቶ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት አበው፣ ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ። መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት፤ ምሳሌም መሰሉላት። ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት።
"እምርሑቅሰ ርእይዋ ወተአምኅዋ" እንዲል።

<3 የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ <3
ከአዳም በሴት
ከያሬድ በሄኖክ
ከኖኅ በሴም
ከአብርሃም በይስሐቅ
ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
ከይሁዳ በእሴይ፣ በዳዊት፣ በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች።

ከሌዊ ደግሞ በአሮን፣ አልዓዛር፣ ፊንሐስ፣ ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች።

አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በአምስት ሺህ አራት መቶ ሰማንያ አምስት ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት፣ ኃጢአት ሳያገኛት፣ ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች።
(ኢሳ. ፩፥፱ ፣ መኃ. ፬፥፯) "ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ።
(ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ)

ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለሦስት ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች። በቤተ መቅደስም ለአሥራ ሁለት ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት ሕብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች። አሥራ አምስት ዓመት በሞላት ጊዜ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት።

በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማኅጸንዋ ጸነሰችው። ነደ እሳትን ተሸከመችው፤ ቻለችው። "ጾርኪ ዘኢይትጸወር ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ።
(ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ)

ወልደ እግዚአብሔርን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጸንሳ እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው።
(ኢሳ. ፯፥፲፬)
"ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በገሊላ ለሁለት ዓመታት ቆዩ።

አርዌ ሄሮድስ እገድላለሁ ብሎ በተነሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም፣ በላበትና በድካም፣ በዕንባና በኀዘን ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ከገሊላ እስከ ኢትዮጵያ ተሰዳለች። ልጇ ጌታችን አምስት ዓመት ከስድስት ወር ሲሆነው ለድንግል ደግሞ ሃያ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ።

በናዝሬትም ለሃያ አራት ዓመት ከስድስት ወር ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች ነዳያንን እያሰበች ኑራለች። እርሷ አርባ አምስት ዓመት ልጇ ሠላሳ ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምህርት፣ ተአምራት ጀመረ። ለሦስት ዓመት ከሦስት ወርም ከዋለበት እየዋለች ካደረበትም እያደረች ትምህርቱን ሰማች።

የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ኀዘን አስተናገደች። አንጀቷ በኀዘን ተቃጠለ። በነፍሷም ሰይፍ አለፈ። (ሉቃ. ፪፥፴፭)
ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሣኤውን አየች። ለአርባ ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች።

ከልጇ ዕርገት በኋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች። በጽርሐ ጽዮንም ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ኖረች። በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ፣ ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል፣ ሐዋርያትን ስታጽናና፣ ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች።

ዕድሜዋ ስልሳ አራት በደረሰ ጊዜ ጥር ፳፩ ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ፤ ኢየሩሳሌምን ጨነቃት። አካባቢውም በፈውስ ተሞላ። በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ። እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ ለዘላለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ፣ ክብርና ተአምራት ዐረፈች። ሞቷ ብዙዎችን አስደንቋል።
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ።" እንዲል።

ከዚህ በኋላ መላእክት እየዘመሩ ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ።
ይህንን ሊቃውንት፦
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ።" ሲሉ ይገልጡታል።

በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው።) እነርሱን ቀጥቶ እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል። በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች።

ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ ፩ ሱባኤ ጀመሩ። ሁለተኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው። እየዘመሩም በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል።

በሦስተኛው ቀን (ነሐሴ ፲፮) እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ ተነስታ ዐርጋለች። ትንሣኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ መግነዟን ተቀብሏል። ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ገቡ።

ለሁለት ሳምንታት ቆይተው ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው። በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ፣ ደስታና ምሥጢርንም አዩ። ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው። የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል።

ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን። አእምሮውን፣ ለብዎውን፣ ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን አክሎግ ቀሲስ፣ መርምሕናም፣ ወዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አክሎግ ሰማዕት <3

ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ይህ ቅዱስ ነው። "አክሎግ" ማለት "በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ (ተወዳጅ)" ማለት ነው። እውነትም ጥዑም ዜና፣ ጣፋጭ ሕይወት ያለው አባት ነው። "መልአክ ስምን ያወጣል።" የሚባለው እንዲህ ላለው ነውና።

እርሱ የወላጆቹ ፍሬ ነው። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ወላጆቹ ለልጃቸው ያወረሱት ሞልቶ የተረፈ ሃብታቸውን አልነበረም። ይልቁኑ ፍቅረ ክርስቶስን፣ ምሥጢረ መጻሕፍትን፣ ክርስቲያናዊ ስምን ነው እንጂ።

ቅዱስ አክሎግ ገና ከልጅነቱ ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሮ፣ ሐዲስ ኪዳንን በሙሉ፣ መኃልየ ነቢያትን፣ መዝሙረ ዳዊትን አክሎ በቃሉ አጠና። ቅዱስ ቃሉ ለእርሱ እውቀት አልነበረም፤ ሕይወት እንጂ። ሳይሰለች ያነበው በሕይወቱም ይተረጉመው ነበርና።

በዚህ ንጹሕ ሕይወቱም ፈጣሪውን አስደስቶ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል። ከዚያም ተጋድሎውን ቀጥሎ በትሕርምት ኑሯል። ቀሲስ ሆኖ ሲሾምም ቅዱሳን መላእክት "ይገባዋል!" ሲሉ ሦስት ጊዜ ጮሁ። በጽድቅ ጸንቶም ዘመናት አለፉ።

በዘመነ ሰማዕታትም ነጭ በነጭ ለብሶ ብዙ መከራን ተቀበለ። በዚህች ቀንም ከብዙ ተከታዮቹ ጋር ደሙ ፈሷል። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን "ጻድቅ፣ ንጹሕ፣ ድንግል፣ ባሕታዊ፣ ቀሲስ ወሰማዕት" ብላ ታከብረዋለች። ጌታም "ስምህን ያከበረውን፣ የተሰየመውን እምርልሃለሁ።" ብሎታል።

<3 ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት <3

ሰማዕቱ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ዐበይት ቅዱሳን አንዱ ነው። በየአብያተ ክርስቲያናቱ ከሚሳሉ ቅዱሳንም አንዱ ነው። ሃገሩ አቶር (በፋርስ አካባቢ) ሲሆን አባቱ ሰናክሬም የሚባል ንጉሠ ነገሥት ነው።

እናቱ ምንም ክርስቲያን ብትሆንም ስለ ፈራች ሁለቱን ልጆቿን (መርምሕናምና ሣራን) ክርስትናን አላስተማረቻቸውም። ሁለቱም ወጣት በሆኑ ጊዜም ከንጉሥ አባታቸው ጋር ይወጡ ይገቡ ነበርና እናታቸው በሐዘን ጸለየች። ወዲያውም ወጣቷ ሣራ በለምጽ ተመታች፤ የሚፈውሳትም ጠፋ። መርምሕናም ግን ጐበዝ ወጣት ነውና አርባ የጦር አለቆችን ይመራ ነበር። በዚያው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ መርምሕናም አርባ ተከታዮቹን ይዞ ለአደን ወደ ዱር ሲወጣ ከአባ ማቴዎስ ገዳማዊ ጋር ተገናኘ።

ጻድቁ ለብዙ ዓመታት በበርሃ የኖሩ አባት ናቸው። አካላቸው በጸጉር ስለ ተሸፈነ ደንግጦ ሲሸሽ "ልጄ አትፍራ! እኔም እንዳንተ የክርስቶስ ፍጡር የሆንኩ ሰው ነኝ።" አሉት።

እርሱ ግን "ደግሞ ክርስቶስ ማነው?" ሲል ጠየቃቸው። አባ ማቴዎስም ምሥጢረ ክርስትናን ከመሠረቱ አስተምረው የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ነገሩት።

ቅዱስ መርምሕናም ግን "ክርስቶስ አምላክ እንደ ሆነ አምን ዘንድ እኅቴን አድንልኝ?" አላቸው። "አምጣት" ብለውት አመጣት። ጻድቁ ጸሎት አድርሰው መሬትን ቢረግጧት ውኃን አፈለቀች። "በእምነት በስመ ሥላሴ ተጠመቁ።" አሏቸው።

ቅዱሱ፣ እኅቱ ሣራና አርባ የጦር አለቆች ተጠምቀው ሲወጡ ሣራ ከለምጿ ነጻች። ፈጽሞም ደስ አላቸው። ወደ ቤተ መንግሥት ተመልሰውም ቅዱስ መርምሕናም ከእናቱ፣ ከእኅቱና ከአርባ ተከታዮቹ ጋር ክርስቶስን ሊያመልኩ ጀመሩ።

ንጉሡ ሰናክሬም ግን ነገሩን ሲሰማ ተቆጣ። እነርሱም ወደ ተራራ ሸሹ። ንጉሡ "ልጆቼ! መንግሥቴን ውረሱ።" ብሎ ቢልክባቸውም እንቢ አሉ። ስለ ተበሳጨም ቅዱስ መርምሕናምን፣ ቅድስት ሣራንና አርባውን ቅዱሳን በሰይፍ አስመታቸው።

ሥጋቸውን በእሳት ሊያቃጥሉ ሲሉ ግን መነዋወጥ ሆኖ ብዙ አረማውያን ሞቱ። ንጉሡም አብዶ አውሬ (እሪያ) ሆነ። ያን ጊዜ አባ ማቴዎስ ከበርሃ ወጥተው ንጉሡን ሰናክሬምን ፈወሱት።

እርሱም አምኖ የልጆቹና የአርባውን ሥጋ በክብር አኖረ። በሃገሩ አቶርም የእመ ብርሃን ማርያምን ቤተ መቅደስ አነጸ። በክርስትና ኑሮም ዐረፈ። እርሱ ከተቀበረ በኋላ ግን የከለዳውያን ንጉሥ መጥቶ አቶርን ወረራት።

ንግሥቲቱን (የቅዱሳኑን እናት) ከሕፃኑ ልጇ ጋርም ገደለ። በኋላም "ለጣዖት ስገዱ።" ማለቱን የሰሙት የቅዱስ መርምሕናም ወታደሮች ደርሰው በምስክርነት ተሰየፉ። ቁጥራቸውም መቶ ሰባ ሺህ ሆነ።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ተአምር ሠሪው ጊዮርጊስ ሆይ! የማስተዋልና የጥበብ መከታ ነህና ደመና ዝናማትን እንደሚያዘንም ፍጹም የሆነ የሕይወት መንፈስ ከፈጣሪ ዘንድ ላክልኝ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን <3

ይህ ቅዱስ ሰው፦
እጅግ የተመሠከረለት ሊቅ፣
በፍጹም ትሕርምት የኖረ ገዳማዊ፣
በርካቶችን ወደ ክርስትና ያመጣ ሐዋርያዊ፣
ለአእላፍ ምዕመናን እረኛ የሆነ የንጽቢን (ሶርያ) ጳጳስ፣
ለጆሮ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን የሠራ ገባሬ መንክራት፣
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንትን ያፈራ ታላቅ መምህር፣
ለክርስቶስና ለእመቤታችን ታጥቆ የተገዛ የፍቅር ሰው፣
ጣቶቹ እንደ ፋና የሚያበሩለት ማኅቶት፣
ራሱን ዝቅ አድርጐ በቆሸሸ ልብስ የሚኖር የትህትና ሰው ነው።

በ፫፻፳፭ (፫፻፲፰) ዓ.ም በኒቅያ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡና አርዮስን ሲያወግዙ እርሱ አንዱ ነበር። በሥፍራውም ሙት አስነስቶ ሕዝቡን አስደምሟል። በዚያም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ሠርቶ ወደ ሃገሩ ተመልሶ በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል።

<3 ደናግል ማርያ ወማርታ <3

በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ "እንተ ዕፍረት - ባለ ሽቱ" ተብለው የሚጠሩ ሁለት እናቶች ነበሩ። ሁለቱም ስማቸው "ማርያም" ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን "ማርያም ኃጥዕት - ከኃጢአት የተመለሰች" ሁለተኛዋን ደግሞ "ማርያም እኅተ አልዓዛር - በቢታንያ የነበረችው" ብለው አበው ይጠሯቸዋል።

በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፪ ቁጥር ፩ ላይ ያለችው የአልዓዛር እኅት (ድንግሊቱ) ናት። ዛሬ የምናስባት ይህችን እናታችንን ነው።

ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተምርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት። ወላጆች ባልነበሩበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል።

በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው። አልዓዛርን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ማርያምና ማርታን ደግሞ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል። ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር።

ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ። በአራተኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርታ በጌታ ፊት ሰግዳ "እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ - አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር።" ብላ አለቀሰች።
(ዮሐ. ፲፩፥፳፩)

ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ። ወዲያውም በሥልጣነ ቃሉ አዝዞ አልዓዛርን አስነሳው። ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ ስድስት ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው።
(ዮሐ. ፲፪፥፩)

በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ ናርዶስ የሚሉትን የሦስት መቶ ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች። መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ" እንዲል ምስጥ የሚያደርግ ሽታ ቤቱን ሞላው።

በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል። ቅድስት ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ" ብሎ አመስግኗታል። ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል።

ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ እናድርግ።" ብሎናል።
(ቅዳሴ ማርያም)
ቅድስት ማርያም በጌታችን ክርስቶስ በኅማሙ ጊዜም ሲቀብሩትም ነበረች። ትንሣኤውንም ዐይታለች።

ከጌታ እርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል አገልግሎት ተግታለች። ቅድስት እናታችን ማርያም እንተ ዕፍረት ዛሬ በዓሏ ከእኅቷ ቅድስት ማርታ ጋር ይከበራል።

የቅዱሳኑ በረከት ይደርብን።

ጥር ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጊዮርጊስ መክብበ ሰማዕታት (ዝርወተ ዓጽሙ)
፪.ቅዱስ ባኮስ ኢትዮጵያዊ (አቤላክ/አቤሜሌክ)
፫.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (ከሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ)
፬.ቅዱሳት ደናግል ማርያ እና ማርታ (ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ
፫.አባ አኖሬዎስ
፬.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

"ጃንደረባውም፦ 'እነሆ ውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?' አለው። ፊልጶስም፦ 'በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዷል።' አለው። መልሶም፦ 'ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ።' አለ። ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ። ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፤ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው። ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም። ደስ ብሎት መንገዱን ይሔድ ነበርና።"
(ሐዋ ፰፥፴፮-፴፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

መክሲሞስና ዱማቴዎስ ግን ምድረ ሶርያ ገብተው የጻድቁ አባ አጋብዮስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ። በእርሱም ዘንድ ለምናኔ የሚያስፈልጉ በጐ ምግባራትንና ትሩፋትን ከተማሩ በኋላ ሁለቱንም አመነኮሳቸው። በዚያ ቦታም እየታዘዙና ፈጣሪን እያመለኩ በጾም፣ በጸሎትና በትህትና ኖሩ።

አንድ ቀን ግን አባ አጋብዮስ ጠርቶ "ልጆቼ! ተባረኩ! በእናንተ ምክንያት ደስ ብሎኛልና። በዚህች ሌሊት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ በራእይ ተገልጦ 'ልጆች እንዲሆኑኝ ስጠኝ።' ብሎኛልና እኔ ሳርፍ ወደ ግብጽ ገዳመ አስቄጥስ እንድትሔዱ።" አላቸው።

አባ አጋብዮስ ካረፈ በኋላ ግን እንደ ትዕዛዙ አልሔዱም። ውዳሴ ከንቱን ይፈሩ ነበርና። በዚያው በምድረ ሶርያ ግን በጥቂት ጊዜ (ገና በወጣትነት) ከብቃት መዓርግ ስለ ደረሱ በርካታ ተአምራትን ሠሩ። በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ ሆኑ።

ስም አጠራራቸውም ሶርያን መላት። በዘመኑ በአካባቢው አንድ ግዙፍ ዘንዶ ተነስቶ ሰውንም እንስሶችንም ፈጃቸው። ሕዝቡም ሒደው በቅዱሳኑ ፊት አለቀሱ። ያን ጊዜ ቅዱስ መክሲሞስ (ትልቁ) ክርታስ አውጥቶ "አንተ ዘንዶ ይህ ክርታስ ወደ አንተ ሲደርስ ከማደሪያህ ውጣ፣ ሙት፤ ወፎችም ይብሉህ።" ሲል ጻፈበት።

"ሒዳችሁ በበሩ ጣሉት።" አላቸው። አንድ ደፋር ሰው ተነስቶ ሰዎች ሁሉ እያዩት ወስዶ በዘንዶው መውጫ ላይ ጣለው። በቅጽበትም ዘንዶው ወጥቶ ሞተ። አሞሮችም ተሰብስበው በሉት። ከዚህ ድንቅ ተአምር የተነሳ ሕዝቡ የቅዱሳኑን አምላክ አከበረ።

ከዚህ በተረፈም በቅዱሳኑ ስም ታላላቅ ተአምራት ተደረጉ። ርኩሳት መናፍስት ሁሉ ስማቸውን እየሰሙ ይሸሹ ነበርና። ድውያን እነሱ በሌሉበት ስማቸው ሲጠራላቸው ይፈወሱ ነበር። የአካባቢው ሰው ስማቸውን እየጠራ በእነርሱም እየተማጸነ ከመከራው ሁሉ ይድን ነበርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሞገስ ሆኑ።

መርከበኞች ደግሞ ከማዕበል ለመዳን የቅዱሳኑን ስም በጀልባዎቻቸው ላይ ይጽፉ ነበር። አንድ ቀን ግን የንጉሡ ለውንድዮስ ባለሟል ይህንን ጽሑፍ ተመልክቶ ስለ ጠረጠረ መርከበኛውን በንጉሡ ፊት አቀረበው።

ንጉሡም መርከበኛውን "የጻፍከው የማንን ስም ነው?" ቢለው "በሶርያ የሚገኙ ሁለት ወንድማማች ቅዱሳን ስም ነው።" አለው። ልጆቹ እንደ ሆኑ ገምቶ በመርከበኛው መሪነት ንግሥቲቱንና ሴት ልጁን ላካቸው። እነርሱ በሐዘን ተሰብረው ነበርና።

ወደ ሶርያ ወርደው ባገኟቸው ጊዜም ከናፍቆትና ደስታ የተነሳ ታላቅ ጩኸትን እየጮሁ አለቀሱ። "ወደ ሮም እንሒድ።" ሲሏቸው ግን ቅዱሳኑ "የለም! እኛ የክርስቶስ ነን።" ብለው እንቢ ስላሏቸው እያዘኑ ተመለሱ። ንጉሡ ግን ይህንን ሲሰማ ደስ አለው። "እነርሱ የዚህን ዓለም ኃላፊነት ተረድተዋል።" ሲልም አወደሳቸው።

በኋላ ግን "የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት መሆን አለባችሁ።" የሚል ነገር ሲሰማ ቅዱሳን መክሲሞስና ዱማቴዎስ ከሶርያ ወጥተው ወደ ግብጽ ወረዱ። ከታላቁ ቅዱስ መቃርስ ዘንድ ደርሰውም ልጆቹ እንዲሆኑ ለመኑት።

"ልጆቼ! በርሃ አይከብዳችሁም?" ቢላቸው "ግዴለም!" አሉት። በዚያም ከተራራው ሥር በዓት ሠርቶላቸው ለሦስት ዓመታት በአርምሞ ቆዩ። አንድ ቀንም ቅዱሳኑ እየጸለዩ ከአፋቸው የወጣ የብርሃን ምሰሶ ከመንበረ ጸባኦት ሲደርስ አይቶ ታላቁ መቃርስ አደነቀ።

በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢም ጥር ፲፬ ቀን ታላቁ ቅዱስ መክሲሞስ ዐረፈ። በዕለቱም የሰማይ ቅዱሳን ሁሉ ወርደው እየዘመሩ ወሰዱት። ከሦስት ቀን በኋላ ደግሞ ቅዱስ ዱማቴዎስ ዐረፈ።

በተመሳሳይ ቅዱሳኑ ሲወስዱት ሁለቱንም ቅዱሳን ታላቁ መቃርስ በበዓታቸው ቀብሯቸዋል። ቦታውም "ደብረ ብርስም (በርሞስ)" ተብሏል። ትርጉሙም "የሮማውያኑ ቅዱሳን ደብር" እንደ ማለት ነው።

አምላከ ቅዱሳን በእነርሱ ላይ የበዛች ፍቅሩን ለእኛም ያድለን። ፍሬ ትሩፋት፣ ፍሬ ክብር እንድናፈራም ይርዳን። ክብራቸውንም አያጉድልብን።

ጥር ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን እና ክቡራን የሚሆኑ አባቶቻችን "መክሲሞስ እና ዱማቴዎስ"

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ (ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
፫.አባ ገሪማ
፬.አባ ጰላሞን ፈላሲ
፭.አባ ለትፁን የዋሕ
፮.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)

"ፍቅር ያስታግሳል፤ ፍቅር ያስተዛዝናል። ፍቅር አያቀናናም፤ ፍቅር አያስመካም። ፍቅር አያስታብይም።
ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም። ክፉ ነገርን አያሳስብም።
ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም።
ሁሉን ይታገሣል፤ ሁሉን ያምናል። ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፤ በሁሉ ይጸናል።"
(፩ቆሮ ፲፫፥፬-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ፊላታዎስ ሰማዕት <3

"ፊላታዎስ" ማለት "መፍቀሬ እግዚአብሔር - እግዚአብሔርን የሚወድ እርሱም የሚወደው" ማለት ነው። ቅዱሱ የዘመነ ሰማዕታት (ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ፍሬ ሲሆን ለየት ያለ ታሪክ ያለው ቡሩክ ወጣት ነው።

እርሱ የባለ ጸጐች ልጅ ስለ ክርስትና ምንም ሰምቶ የማያውቅ ሕፃን ነበር። ወላጆቹ የሚያመልኩት ላምን ሲሆን የአካባቢው ሰው ደግሞ ለፀሐይ ይንበረከክ ነበር። ቤተሰቦቹ ስለ አምልኮ ሲጠይቁት "እናንተ የምታመልኳቸው ፍጡራን ስለ ሆኑ አልፈልግም።" አላቸው።

ሕፃን ቢሆንም ስለ ፈጣሪው ተመራመረ። በመጨረሻውም ፀሐይን "አንተ ምንድነህ?" ቢለው "እኔ ፍጡር ነኝ።" ሲል መልሶለታል። በዚያች ዕለት ግን ቅዱስ መልአክ ወርዶ ሁሉን ነገር አስተምሮ የክርስቶስ ወታደር አድርጐታል።

ወደ ቤቱ ተመልሶም የወላጆቹን ላም "እውነትን ተናገር።" ብሎ ገስጾታል። ላሙም ሰይጣን እንዳደረበት በሰው ልሳን ተናግሮ የቅዱሱን ወላጆች ወግቶ ገድሏቸዋል። ቅዱስ ፊላታዎስ ግን ላሙን አስገድሎ ወላጆቹን ከሞት አስነስቶ ከአካባቢው ሰው ጋር በስመ ሥላሴ አስጠምቋቸዋል።

በድንግልና ኑሮም ዘመነ ሰማዕታት ሲጀምር በርጉም ዲዮቅልጥያኖስ እጅ ብዙ ተሰቃይቷል። በጸሎቱም ጣዖታቱን (እነ አጵሎንን) ከነ አገልጋዮቻቸው ወደ ጥልቁ አስጥሟቸዋል። እርሱም በዚህች ቀን በሰይፍ ተከልሎ ለክብር በቅቷል። ለእኛ ለኃጥአን የሚሆን ቃል ኪዳንንም ከጌታው ተቀብሏል።

የቅዱሳን አባቶቻችን አማናዊት ርስት ድንግል ማርያም አትለየን።

ጥር ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ፊላታዎስ ሰማዕት
፪.አባ ጰላድዮስ ገዳማዊ
፫.ማር ዳንኤል ሶርያዊ
፬.አባ ዮሐንስ መሐሪ (ሊቀ ጳጳሳት)
፭.አሥራ አንድ ሺህ አራት ሰማዕታት (የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበር)
፮.አሥር ሺህ አምስት መቶ ሦስት ሰማዕታት (የቅዱስ ፊላታዎስ ማኅበር)
፯.አባ ጽሕማ (ከተስዓቱ ቅዱሳን አንዱ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓለ ኪዳና ለድንግል
፪.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፬.ቅድስት ኤልሳቤጥ
፭.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ

"ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል። እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል።
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል። በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።
ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ። ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ።"
(መዝ ፺፩፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቂርቆስ ወኢየሉጣ <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው። በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው።
ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦ "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል።"
(ማቴ. ፯፥፲፯)

መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብፁዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል። ቡርክተ ማኅጸንም እንላታለን። የተባረከ ማኅጸኗ የተባረከ ልጅን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተሸክሟልና።

በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕፃን እርሷን መስሎ እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና። አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብፁዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች።

በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ። በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር።

ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት። መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኳ የመጮህ እድል አልነበረውም። ምክንያቱም የሚሰማው የለም።

በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ። የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር። ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ ካልሆነ ደግሞ ሃገሩ ጥሎ በዱር በገደል መሰደድ ነበረበት።

እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም። ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና።

ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብፅዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) ፍሬ ናቸው። በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ። ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው።

በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት (ኢጣልያዊት) ብፅዕት ኢየሉጣም በመበለትነት (ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ) ትኖር ነበር። ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና ሦስት ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር።

እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕፃን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች። ሃብት ንብረቷን፣ ወገንና ርስቷንም ትታ ሕፃን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች። መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም።

እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት። ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት። መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ?" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው።" አለችው። ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ?" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው። ሞክሼ (ሞክሲ) ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ።" አለችው።

"ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል።" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የሦስት ዓመት ሕፃን ፈልገህ አምጣና ተረዳ።" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው። የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር።

ቅዱሱ ሕፃን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕፃን - ደስ የተሰኘህ ሕፃን እንዴት ነህ?" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታዬ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል። አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ።" አለው።

በሕፃኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ?" አለው። ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ስሜ ክርስቲያን ነው። እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው።" ሲል መለሰለት።

ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ።" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕፃን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ። ከዚህ በኋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር (እጽፍ) ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም።

በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ።
ሰባት ብረት አግለው በዓይናቸው፣ በጆሯቸው፣ በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ።
በአራት ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው።
በእሳት አቃጠሏቸው።
ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ። ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው።

እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ። ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕፃኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል። ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል።

<3 ቅዱስ አብድዩ ነቢይ <3

"አብድዩ" ማለት "የእግዚአብሔር አገልጋይ" ማለት ነው። ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን የቅዱስ ኤልያስ ታላቁም ደቀ መዝሙር ነው። ቅዱሳን ነቢያት ዮናስና ኤልሳዕም ባልንጀሮቹ ነበሩ።

ቅዱስ አብድዩ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንት ዓመት አካባቢ የከሃዲው ንጉሥ የጦር መሪ ሆኖ በሃምሳ አለቃነት አገልግሏል። ግፈኛዋ ኤልዛቤል ነቢያተ እስራኤልን ስታስፈጅ ሃምሳውን በአንድ ዋሻ ሃምሳውን ደግሞ በሌላ ዋሻ አድርጐ አትርፏቸዋል። ዘጠኝ መቶው ግን ተጨፍጭፈዋል።

ያተረፋቸውንም ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ መግቧቸዋል። አክአብና ኤልዛቤል ከሞቱ በኋላም ቅዱስ ኤልያስን ተከትሎ ሹመቱን ትቷል። እግዚአብሔር ገልጾለትም ትንቢት ሲናገር ሕዝቡንም ሲገሥጽ ኑሯል።

በብሉይ ኪዳን ካሉ የትንቢት መጻሕፍትም በጣም አጭሩን የጻፈው ይህ ነቢይ ነው። ትንቢተ አብድዩ ባለ አንድ ምዕራፍ ብቻ ናትና። ቅዱሱ በዚህች ቀን ዐርፎ ወገኖቹ ቀብረውታል።

አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን። በይቅርታው ኃጢአታችንን ይተውልን። ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን።

ጥር ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ አብድዩ ነቢይ
፫.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
፬.ቅድስት ሶፍያ
፭.ቅድስት አድምራ
፮.አሥራ አንድ ሺህ አርባ አራት ሰማዕታት (ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር በሰማዕትነት ያለፉ።)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
፪.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፫.ቅድስት ክርስጢና
፬.ቅድስት እንባ መሪና

"በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ በልብህም 'ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው?' የምትል አንተ ሆይ! የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን 'ከዚያ አወርድሃለሁ።' ይላል እግዚአብሔር።"
(አብድዩ ፩፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና አባ አርከሌድስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ <3

ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮጵያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት። አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው።

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው። በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር፦
፩.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ፣
፪.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግሥት) እና
፫.ገዳማዊ ሕይወት ነው።

አቡነ አረጋዊን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግሥት ነው። እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል። አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል።

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ጰንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ። ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ።

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮጵያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም። ስለዚህም በ፬፻፸ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮጵያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ።

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው። ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው። ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች። አቡነ አረጋዊና ስምንቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር።

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዚያው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ። በወቅቱ በአቡነ ሰላማ፣ በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አቡነ አረጋዊ እንደገና አቀጣጠሉት።

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት። የካደውን እየመለሱ የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ።

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው። በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አቡነ አረጋዊ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማኅበር ነበር። በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም።

የነ አቡነ አረጋዊ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ። ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው። እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ።
ጰንጠሌዎን በጾማዕት፣
ገሪማ በመደራ፣
ሊቃኖስ በቆናጽል፣
አባ ይምዓታ በገርዓልታ፣
ጽሕማ በጸድያ፣
ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ።
አባ አረጋዊ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ዳሞ (እዚያው ትግራይ) ሆነ።

በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው። ጻድቁ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ንጉሥ ይስሐቅና ቅድስት እድና ይባላሉ። የተለወለዱበት አካባቢም ሮም ነው።

ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው። ወላጆቻቸው "ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ።

በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ጳኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል። ከመነኮሱ ከዓመታት በኋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር ሰባት ያህል የቤተ መንግሥት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል።

"የት ልሒድ?" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮጵያን አሳያቸው። ተመልሰውም ለስምንት ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየኋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር።" ብለው ከስምንቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጡ።

በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ። ወደ ሃገራችን የመጡ በ፬፻፸ዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል። በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ፣ ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል።

ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል። በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን (ደብረ ሃሌ ሉያን) አይተው ወደዷት። የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ ስልሳ ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል።

እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል። በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች። ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በኋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው ስድስት ሺህ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል።

ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮጵያ - የኢትዮጵያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል።

ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ። በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው ንግሥት እድና ሁናለች።

ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመታቸው በገዳሙ በስተ ምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል። ጌታም አሥራ አምስት ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። ዛሬ ጻድቁ የተወለዱበት ቀን ነው።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ ዘርዓ ቡሩክ እና ሰባቱ ደቂቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ ዘርዓ ቡሩክ <3

ሃገራችን ኢትዮጵያ ብሉይ ከሐዲስ ያልጐደለባት በክርስቶስና በድንግል እናቱ ኪደተ እግር የተቀደሰች የቅዱሳን መጠጊያ እና ብዙ ቅዱሳንን ከእቅፏ ያፈራች ስለ ሆነች የተባረከች ሃገር ትባላለች።

ሁሉም የሃገራችን ክፍሎች ቅዱሳንን አፍርተዋል። በምሥራቅም፣ በምዕራብም፣ በሰሜንም፣ በደቡብም ያሉ አካባቢዎች ሁሉ የቅዱሳን ቤቶች ናቸው። ቅዱሳንን በብዛት ካፈሩ አካባቢዎች አንዱ ደግሞ ምድረ ጐጃም ነው።

በጐጃም አካባቢ ከተነሱ ቅዱሳን ደግሞ አንዱና ስመ ጥሩ ጻድቅ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ናቸው። አቡነ ዘርዓ ቡሩክ በብዙ ጐዳና የተለዩ አባት ናቸው። ለመጥቀስ ያህል እንኳ፦
፩.በታሪክ ዓለምን ከበው የያዙ ሁለቱ ግሩማን አራዊት (ብሔሞትና ሌዋታንን) ጥርስ ቆጥረው ብዙ ምሥጢራትንም ተመልክተው ተመልሰዋል። (በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ሳይንሱ በብዙ ድካም ያልደረሰበት ነው።)
፪.ጻድቁ በልደታቸው ጊዜ ዓይነ ስውራንን አብርተዋል። ለራሳቸው ግን ይህን የግፍ ዓለም ላለማየት ጸልየው ዓይናቸው እንዲጠፋ አድርገዋል።
፫.መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል ቅዱስ ኢያሱ በገባኦን ፀሐይን አቁሟል። ዘርዓ ቡሩክ ግን በጥበበ እግዚአብሔር ፀሐይን ለአምስት ዓመት አቁመዋል።
፬.ጻድቁ ከንጽሕናቸው ብዛት አሥራ ሁለት ክንፍ (መንፈሳዊ ክንፍ) ተሰጥቷቸው ነበር። ከዚህ በተረፈም በጾም፣ በጸሎት፣ በትሕርምትና በስብከተ ወንጌል ፍጹም ጽሙድ ነበሩ።

ጻድቁ የተወለዱት በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እዚያው ጐጃም ውስጥ ሲሆን አባታቸው ደመ ክርስቶስ እናታቸው ደግሞ ማርያም ሞገሳ ይባላሉ። ወላጆች በልጅ እጦት ተማለው ይህን የተቀደሰ ፍሬ አገኙ። "ጸጋ ኢየሱስ" ብለውታል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቷቸዋልና።

ቀጥሎ የወለዱትንም "ተስፋ ኢየሱስ" ብለውታል። ይህም የጻድቁ ታናሽ ወንድም ነው። በሒደት ግን የጸጋ ኢየሱስ ስም በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ዘርዓ ቡሩክነት ተቀይሯል። ጻድቁን ስመ ጥር ካደረጓቸው ሥራዎቻቸው መካከል በአፄ ሱስንዮስ ዘመን የሠሩት ቅድሚያውን ይወስዳል።
ነገሩ እንዲህ ነው።
በ፲፭፻፺፰ ዓ/ም በኢትዮጵያ ላይ የነገሡት አፄ ሱስንዮስ ጴጥሮስ ፓኤዝ (ፔድሮ ፓኤዝ) ከሚባል ፈረንጅ መናፍቅ ጋር በፈጠሩት ወዳጅነት ሃይማኖታቸውን ለወጡ። ካቶሊክ (ሮማዊ)ም ሆኑ።

በኋላም አልፎንሱ ሜንዴዝ የሚሉት እሾህ መጥቶ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ መናፍቅ እንዲሆን ከንጉሡ ጋር መከረ። ለጊዜው በቤተ መንግሥቱ አካባቢ የነበሩ መሳፍንት ተቀላቀሉ። እየቆየ ግን ዜናው በመላ ሃገሪቱ ተሰማ።

በተለይ ከ፲፮፻፱ - ፲፮፻፲፮ ዓ.ም በተዋሕዶ አማኞችና በመናፍቁ ንጉሥ መካከል ነገሩ ተካሮ ጳጳሱ አቡነ ስምዖን ጠዳ ላይ መገደላቸው ተሰማ። በዚህ ጊዜ ገበሬው ከእርሻው፣ ሴቷ ከማዕድ ቤት፣ ካህኑ ከመቅደሱ፣ ነጋዴው ከገበያው እየወጡ ስለ ቀናችው ሃይማኖት ደማቸውን አፈሰሱ።

በበዓት የተወሰኑ በሺህ የሚቆጠሩ ቅዱሳንም ወጥተው ተሰየፉ። በዚህ ጊዜም የግሺው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ዳዊታቸውን አንግበው ለሰማዕትነት ሔዱ። ዓባይ ወንዝ ላይ ሲደርሱ ዳዊታቸውን ወደ ወንዙ ውስጥ ጣሉት።

ተሻግረውም ከንጉሡ አደባባይ ደንቀዝ ደረሱ። በጊዜውም ልክ እንደነ ፍቅርተ ክርስቶስና ወለተ ጴጥሮስ እርሳቸውም መከራ ደረሰባቸው። ንጉሡም ሳይገደሉ እንዲታሠሩ አደረገ። በጨለማ እስር ቤትም አምስት ዓመታትን ሲያሳልፉ ትኩስ ምግብን ያመጡላቸው ነበር።
እርሳቸው ግን ምግባቸው ሰማያዊ ነበርና አልነኩትም። ከአምስት ዓመት በኋላም ያ ሁሉ ምግብ በተአምራት በትኩስነቱ እየጨሰ ተገኝቷል። ዘርዓ ቡሩክም ከእሥር ተፈትተዋል።

እግዚአብሔርም በከሐዲው ንጉሥ ላይ ፈርዶ ፋሲል ነግሷል፤ ሃይማኖት ተመልሷል። ጻድቁም በዓባይ ወንዝ ላይ የጣሉት ዳዊታቸውን ሳይርስ አግኝተውታል።

ጐጃም ሲደርሱም ሰይጣን እርሳቸውን መስሎ ሲያስት ስላገኙት ወደ ጥልቁ አስጥመውታል። በተረፈ ዘመናቸው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ብዙ ተጋድለው ጥር ፲፫ ቀን ዐርፈዋል።
ድንቅ ሠሪ አባት ናቸውና ዛሬም በግሺ ብዙ ተአምራት ይደረጋሉ!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቃና ዘገሊላ እና ለቅዱሳን ያዕቆብ ወቴዎድሮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቃና ዘገሊላ <3

"ቃና" የሚለው ቃል በሃገራችን ልሳን (በአማርኛ) የምግብን፣ የመጠጥን ጥፍጥና ወይም በጐ መዓዛን የሚያመለክት ነው። ምናልባትም ከዚህ በዓል ምሥጢር የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ግን ቃና ከገሊላ አውራጃዎች አንዷ ናት። ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ በዚህች ሥፍራ ተገኝቶ በድንግል እናቱ ምልጃ ታላቅ ተአምርን በዚህች ዕለት ሠርቷል።

"ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል። መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው (Miracle) የሚሉት ዓይነት ነው። ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ) ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል።

ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው። ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ /ከሐሌ ኩሉ/ ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው።

እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል። በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ፣ መና ሲያዘንሙ፣ ውኃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት።) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ፣ እሳትን ሲያዘንሙ፣ ሙታንን ሲያስነሱ (፩ነገሥትን ተመልከት።) እንደ ነበር ይታወቃል።

እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል። በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል።
(ማቴ. ፲፥፰ ፤ ፲፯፥፳ ማር. ፲፮፥፲፯ ፣ ሉቃ. ፲፥፲፯ ዮሐ. ፲፬፥፲፪)
እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል።
(ሐዋ. ፫፥፮ ፤ ፭፥፩ ፤ ፭፥፲፪ ፤ ፰፥፮ ፤ ፱፥፴፫-፵፫ ፤ ፲፬፥፰ ፤ ፲፱፥፲፩)

ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ በወንጌሉ ምዕራፍ ፪ ላይ እንዳስቀመጠው የቃና ዘገሊላው ተአምር የመጀመሪያው ነው። "ወዝንቱ ቀዳሜ ተአምር....." እንዲል።
(ዮሐ. ፪፥፲፩)
ያ ማለት ግን ጌታ ከዚያ በፊት ተአምራትን አልሠራም ማለት አይደለም።
ይልቁኑ ራሱን ከገለጠና ከተጠመቀ በኋላ የሠራው የመጀመሪያው ተአምር ነው ሲል ነው እንጂ። ምክንያቱም መድኃኒታችን እንደ ተጠመቀ ዕለቱኑ ገዳመ ቆረንቶስ ገብቷልና።
(ማቴ. ፬፥፩)
አንድም በቃና ሌሎች ተአምራትን የሚሠራ ነውና ይህ ተአምር በቃና የመጀመሪያው ሆነ።

ትክክለኛው የቃና ዘገሊላ ቀን የካቲት ፳፫ ነው። ጥር ፲፩ ተጠምቆ የካቲት ፳፩ ቀን ከጾም ተመልሷል። ከዚያም የካቲት ፳፫ ቀን ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ሒዷል። ነገር ግን አበው መንፈስ ቅዱስ እንደ መራቸው የውኃ በዓል ከውኃ በዓል ጋር ይስማማል ብለው ጥር ፲፪ አድርገውታል።

በቃና ዘገሊላ ሙሽራው ዶኪማስ ሲሆን ባለ ሠርጉ ደግሞ አባቱ ዮአኪን ነው። ይህም ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል አጐቱ ነው። የልጁ ጋብቻ የተቀደሰ ይሆን ዘንድም ጌታ ክርስቶስን፣ ድንግል እናቱንና ባለሟሎቹ ሐዋርያትን ወደ ሠርጉ ጠራ።

ምንም እንኳ መድኃኒታችንና እመቤታችን ከድግሱ የማይበሉ ቢሆኑም (በትሕርምት ኗሪዎች ነበሩና።) ጠሪውን ደስ ለማሰኘት ሠርጉን ለመቀደስና የጋብቻን ክቡርነት ለማሳየት አብረው ታደሙ።

የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ሲጀመር በድንኳኑ ውስጥ ጌታ ከመካከል ተቀመጠ። ድንግል በቀኙ፣ ዮሐንስ በግራው ሲቀመጡ፣ ሌሎች ሐዋርያት ግራና ቀኝ ከበው ተቀመጡ። ሲበላና ሲጠጣ ድንገት የተደገሰው ምግብና መጠጥ አለቀ።

ደጋሾቹ በጭንቅ ላይ ሳሉም አይጠና ሆዷ ድንግል እመ ብርሃን የሆነውን አወቀች።
እንዴት አወቀች ቢሉ፦ በጸጋ፣ አንድም "ከልጅሽ አማልጂን።" ብለው ቢለምኗት ነው ይሏል። እመቤታችን በዚያ ጊዜ ወደ ልጇ ቀርባ ቸር ልጇን "ወይንኬ አልቦሙ - ወይኑኮ አልቆባቸዋል።" አለችው።

ለጊዜው ወይኑም፣ ምግቡም ስላለቀባቸው እንዲህ አለች። በምሥጢሩ ግን ወይን ያለችው ፍቅርን፣ ቅዱስ ቃሉንና ክቡር ደሙን ነው። ጌታም ይመልሳል፦ "ምንት ብየ ምስሌኪ ኦ ብእሲቶ ዓዲ ኢበጽሐ ጊዜየ - አንቺ ሆይ! (እናቴ ሆይ!) ያልሽኝን አላደርግ ዘንድ ካንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ? ነገር ግን ጊዜው ገና አልደረሰም ብየ ነው እንጂ።" አላት።

ምክንያቱም ጌታ
የወይን ጋኖቹ እስኪያልቁ ይጠብቅ ነበር። (አበረከተ ይሉታልና።)
አንድም ይሁዳ ወጥቶ ነበርና እርሱ እስኪመለስ ነው። (እኔ ስወጣ ጠብቆ ተአምር ሠራ ብሎ ለክፋቱ ምክንያት እንዳያቀርብ።)
አንድም "ወይን (ቅዱስ ደሜን) የምሰጠው በቀራንዮ አንባ ነው።" ሲል "ጊዜዬ ገና ነው።" ብሏታል። አንዳንድ ልቡናቸው የጠፋ ወገኖቻችን ጌታ እመቤታችንን እንዳቃለላት (ሎቱ ስብሐት! ወላቲ ስብሐት!) አስመስለው ይናገራሉ።

ይህንን እንኳን ጌታ ባለጌዎቹ እነርሱም አያደርጉት። "አባትህንና እናትህን አክብር።" (ዘጸ. ፳፥፲፪) ያለ ጌታ እንዴት ለእናቱ ክብርን ይነፍጋል?
ልቡና ይስጠን!

ወደ ጉዳያችን ስንመለስ መድኃኒታችን እንዲህ ሲል መለሰላት። ተግባብተዋልና እመ ብርሃን አሳላፊዎቹን "ኩሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ - የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ።" አለቻቸው።
(ዮሐ. ፪፥፭)
ጌታም በስድስቱ ጋኖች ውኃ አስሞልቶ በተአምራት ወይን አደረጋቸው።

እንጀራውን ወጡን በየሥፍራው ሞላው። ታላቅ ደስታም ሆነ። የአሳላፊዎቹ አለቃም (ለአባታችን አብርሃም ምሳሌ ነው።) ከወይኑ ጥፍጥና የተነሳ አደነቀ። በዚህም የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የመድኃኒታችን ከሃሊነት ታወቀ፤ ተገለጠ።

<3 ቅዱስ ያዕቆብ ርዕሰ አበው <3

የአባቶች አለቃ የተሰኘ ቅዱስ ያዕቆብ ለሁለቱ ታላላቅ አባቶቹ እርሱ ሦስተኛቸው ነው። እነርሱን መስሎ እነርሱንም አህሎ በጐዳናቸው ተጉዟል። በፈቃደ እግዚአብሔር ብኩርናን ከኤሳው ተቀብሎ ወደ ሶርያ ሲሸሽ ቤቴል (ፍኖተ ሎዛ) ላይ ድንጋይ ተንተርሶ በተኛበት ግሩም ራእይን አይቷል።

ይህችውም የወርቅ መሰላል የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት።
"አንቲ ውዕቱ ሰዋስው ዘርእየ ያዕቆብ" እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም።
(ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ)
ተነስቶም "ዛቲ ይእቲ ኈኅታ ለሰማይ ዝየ ይትሐነጽ ቤተ እግዚአብሔር - ይህች የሰማይ ደጅ ናት። ቤተ እግዚአብሔርም ይታነጽባታል።" ብሎ ትንቢት ተናግሯል።

ይህ ቅዱስ አባት ለድንግል ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን፣ ካህናትን፣ ነገሥታትንና መሳፍንትን ወልዷል። ከሁለቱ ሚስቶቹ (ልያና ራሔል)፣ ከሁለቱ ደንገጥሮች አሥራ ሁለት ልጆችን ወልዷል።

ከአጐቱ ከላባ ዘንድ ለሃያ አንድ ዓመታት አገልግሎ ሃብት ንብረቱን ጠቅልሎ ወደ ርስቱ ከነዓን ሲመለስ ለብቻው ራቅ ብሎ ይጸልይ ገባ። በዚያም እግዚአብሔር ሲታገለው አደረ። ይኸውም የፍቅርና የምሥጢር ነው። ለጊዜው ጌታ ያዕቆብን "ልቀቀኝ" ቢለው "ካልባረከኝ አለቅህም።" አለው። ጌታም ስሙን "እስራኤል" ብሎ ባርኮታል።

ቅዱስ ያዕቆብ በስተእርጅና ብዙ መከራ አግኝቶታል። ልጁን ዮሴፍን ወንድሞቹ ሽጠው "አውሬ በላው።" ብለውታልና በለቅሶ ዓይኑ ጠፋ። በረሃብ ምክንያትም በመቶ ሠላሳ ዓመቱ ከሰባ አምስት ያህል ቤተሰቦቹ ጋር ወደ ግብጽ ወረደ። በዚያም ለሰባት ዓመታት ኑሮ በመቶ ሠላሳ ሰባት ዓመቱ ዐርፏል። ልጆቹም ቀብረውታል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ <3

ቅዱስ ወንጌል ላይ ቅዱስ ሉቃስ "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል።
(ሉቃ. ፩፥፮)

እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና የዘካርያስ ደግሞ መቶ ደርሶ ነበር።

ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው።

ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች። በስድስተኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው።

የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ ሰኔ ፴ ቀን ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል።

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእስራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሄሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕፃን አለና እሱንም ግደል።" አሉት።

እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል። አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለሦስት (አምስት) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ አምስት (ሰባት) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት።

ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው። እርሷም ስደት ላይ ነበረችና። ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው። ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው። ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ።" አላት። ባርካው፣ አጽናንታውም ተለያዩ።

ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ። ለሃያ አምስት (ሃያ ሦስት) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም። ይህችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም።

ከዚህ በኋላ ሠላሳ ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው። "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ።" አለው። ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና።
(ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩)
አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. ፩፥፸፮) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና።

ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ። ያዩት ሁሉ ፈሩት፤ አከበሩት። ቁመቱ ቀጥ ያለ፣ ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ፣ ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ፣ መልኩ የተሟላ፣ ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና።

ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ። ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው። በዚህ አገልግሎት ለስድስት ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ "አጥምቀኝ" ብሎ ሲመጣ ደነገጠ፤ የሚገባበትም ጠፋው።

"እንቢ ጌታዬ! አንተ አጥምቀኝ?" አለው። ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው፤ አጠመቀው። በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል። ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሄሮድስን ገሰጸው። ንጉሡም ተቀይሞ ለሰባት ቀናት አሠረው።

ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሄሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው። እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት።
አበው "እምሔሶ ለሄሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሄሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር።" ይላሉ። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል።
(ማቴ. ፫፥፩ ፣ ማር. ፮፥፲፬ ፣ ሉቃ. ፫፥፩ ፣ ዮሐ. ፩፥፮)

"አስማተ ዮሐንስ መጥምቅ - የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች"
፩.ነቢይ
፪.ሐዋርያ
፫.ሰማዕት
፬.ጻድቅ
፭.ካህን
፮.ባሕታዊ / ገዳማዊ
፯.መጥምቀ መለኮት
፰.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
፱.ድንግል
፲.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
፲፩.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
፲፪.መምሕር ወመገሥጽ
፲፫.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

አምላከ ቅዱሳን በጥምቀቱ ይቀድሰን። ከበረከተ ጥምቀቱም ያድለን።

ጥር ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.በዓለ ኤጲፋንያ
፪.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
፫.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
፬.አባ ወቅሪስ ገዳማዊ
፭.አባ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት
፮.ቅዱስ እንጣልዮስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፬.ቅድስት ሐና ቡርክት

"ጌታ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ። እነሆም ሰማያት ተከፈቱ። የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ። እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ 'በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው።' አለ።"
(ማቴ ፫፥፲፮-፲፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጾመ ገሃድ እና አባ ታውብንስጦስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጾመ ገሃድ <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው ሰባት አጽዋማት አሏት። "ጾም" ማለት "መከልከል" ነው። የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ መባልዕት መከልከልን ይመለከታል።

"ሰባቱ" አጽዋማት፦
፩.ዓቢይ ጾም
፪.ጾመ ፍልሠታ
፫.ጾመ ሐዋርያት
፬.ጾመ ነቢያት
፭.ጾመ ድኅነት
፮.ጾመ ነነዌ እና
፯.ጾመ ገሃድ ይሰኛሉ።

በእነዚህ አጽዋማት ከዓቢይ ጾም በቀር እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ መጾም ይገባል። ዓቢይ ጾም ግን የተለየ ሥርዓት አለውና ይቆየን። ስለ ጾም ሲነሳ አስቀድሞ የሚመጣው ጥያቄ አስፈላጊነቱ ነው። "ጾም ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ ከመጠየቅ "ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ መጠየቁ ይቀላል።

ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ትዕዛዛት ትልቁ በመሆኑ እርሱን መቃወም ሃይማኖትንና አዛዡን እግዚአብሔርን መቃወም ነውና። እኛ ሃገር ላይ የተለመደች ክፉ ልማድ አለች። የከበደችንን ነገር "አያስፈልግም" በሚል እንከራከራለን።

ደግሞ ጾምን ለመሻር ጥቅስ የሚጠቅሱ ወገኖች በጣም ይገርሙኛል። ኃጢአትን ለመሥራት ጾምንም ለመሻር ጥቅስን መጥቀስ አያስፈልግም። እኛ ግን ከፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ (ማቴ. ፬፥፪) አበው ቅዱሳን ጾመው (ዘዳ. ፱፥፲፱ ፣ ፩ነገ. ፲፱፥፰ ፣ ሐዋ. ፲፫፥፫ ፣ ፩ቆሮ. ፬፥፲፩) አሳይተውናልና እንደ አቅማችን እንጾማለን።

"ገሃድ" የሚለው ቃል በቁሙ "መገለጥን፣ መታየትን፣ ይፋ መሆንን" የሚያመለክት ሲሆን በምሥጢሩ ግን "የማይታይ አምላክ መታየቱን፣ የማይዳሰሰው መዳሰሱን" ያመለክታል።
ወይም በሌላ ልሳን ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም በተዋሕዶ ሰው ከሆነ በኋላ ለሠላሳ ዓመታት ራሱን ሳይገልጥ ቆይቶ ነበርና በሠላሳ ዓመቱ ራሱን ለእስራኤል በዚህ ሰሞን መግለጡን ልብ የምንልበት በዓል ነው።

መድኃኒታችን ሁሉን ነገር የሚሠራው በጊዜው ነውና ከሥጋዌው በኋላ ለሠላሳ ዓመታት ከስደት መልስ ደግሞ ለሃያ አምስት ዓመታት የሰውነቱን ምሥጢር በይፋ ሳይገልጥ ቆይቷል። ያም ሆኖ የሰውነቱን ምሥጢር እርሱ፣ የባሕርይ አባቱና ቅዱስ መንፈሱ ለድንግል ማርያም ገልጠውላት ታውቀው ነበር። እርሷ ግን መዝገበ ምሥጢር ናትና ሁሉን ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር።
(ሉቃ. ፪፥፶፪)

መድኃኒታችን ከሥጋዌው (ሰው ከሆነባት) ደቂቃ ጀምሮ መግቦቱን አላቋረጠም። ምንም በግዕዘ ሕፃናት ቢኖርም እርሱ በዘባነ ኪሩብ የሚሠለስ ቸር ጌታ ነውና መግቦናል።

እንደ እስራኤል ባህል ሠላሳ ዓመት በሞላው ጊዜ ግን ሥግው አምላክ መሆኑን ገለጠ። የተገለጠውም በጥምቀቱ ሲሆን በዕለቱ ከአብ፣ ከመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ልጅነቱን አስመስክሯል። በባሪያው በዮሐንስ እጅም ተጠምቆ ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶልናል።

የእዳ ደብዳቤአችንን ቀዶ ልጅነታችንን መልሶልናል። ይህ ሁሉ የተደረገ ለእኛ ነውና በዓለ ኤጲፋንያን (ዕለተ አስተርእዮቱን) በድምቀት እናከብራለን።

ነገር ግን ልክ በቅርብ ጊዜ እያየነው እንደሚገኘው በዘፈንና ከአምልኮ ባፈነገጠ መንገድ እንዳይሆን ቤተ ክርስቲያን አበክራ ታሳስባለች። የመድኃኒታችንን የማዳን ሥራ ከማዘከርና ለእርሱ ከመገዛት ይልቅ ራስን ዘፈን በሚመስል መዝሙር መቃኘቱና ለልብስ ፋሽን መጨነቁ የሚጠቅም አይደለም።

በዓላት በሚዲያ ታዩ፣ ተመዘገቡ ብለን ከመዝናናት ትውፊታችንን እያጠፉ ያሉ ድርጊቶቻችን ብንታዘባቸውና ብናርማቸው ይመረጣል። ስኬታችን ሁሉም ክርስቲያን ለእግዚአብሔር መንግሥት መብቃቱ እንጂ በዓል አከባበራችን ዝነኛ መሆኑ አይደለም።

ጉዳዩ መለኮታዊ እንጂ ፖለቲካዊ አይደለምና ጥንቃቄን ይሻል። ዛሬ ለታቦተ እግዚአብሔር ክብርን የማይሰጥና ተጋፊ ትውልድን እየፈጠርን ነው። ካህናትን አለመስማትና ታቦታትን አግቶ አላስገባም ማለት በክርስትና ትርጉሙ ከሰይጣን መወዳጀት ነው። ስለዚህም በዓል አከባበራችንን እንታዘብ፤ ደግሞም እናርመው።

ቤተ ክርስቲያን ጾመ ገሃድን የደነገገች ለሦስት ምክንያት ነው።
፩.የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጥሙና እያሰብን በጾም እንድናመልከው።
፪.በዓል አከባበራችን እንደ አሕዛብ በተድላ ሥጋ፣ በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳይሆንና ሰውነታችንን በጾም እንድንገራው።
፫.ልደትና ጥምቀት ረቡዕና ዓርብ ሲውሉ እህል በነግህ (በጧት) መቀመስ ስላለበት የእርሱ ቅያሪ (ተውላጥ) እንዲሆን ነው።

ጾመ ገሃድን የሠሩት አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ ያጸኑት ደግሞ ቅዱሳን ሊቃውንት ናቸው። አጿጿሙም ጥምቀት ከማክሰኞ እስከ ቅዳሜ ከዋለ በዋዜማው "እስከ ይሠርቅ ኮከብ" እንዲሉ አበው እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ ይጾማል።

በዓለ ጥምቀት እሑድ ሲሆን ዓርብን አዘክሮ በዕለተ ቅዳሜ ደግሞ ከጥሉላት ተከልክሎ መዋል ይገባል። በተመሳሳይ ሰኞ ቢውል ዓርብን አዘክሮ ቅዳሜና እሑድን ከጥሉላት (ከሚያገድፉ ምግቦች) ሁሉ ተከልክሎ መዋል ይገባል።

ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ነውና የተለየ ግለሰባዊ ችግር እስከሌለ ድረስ ሊጾም ግድ ይላል፣ ችግር ካለ ደግሞ ከንስሐ አባት ጋር ሊመክሩ ይገባል።

<3 አባ ታውብንስጦስ ዘሲሐት <3

በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም የተነሳ
ከልጅነቱ መጻሕፍትን የተማረ፣
በክህነት አገልግሎቱ ለብዙዎች አባት የሆነ፣
በምናኔ ወደ ግብጽ የወረደ፣
በእስክንድርያ አካባቢ አበ ምኔት ሆኖ ብዙ መነኮሳትን የመራ፣
በዘመነ ሰማዕታት የተሰደደ፣
ብዙ አሕጉራትን ዞሮ ያስተማረ፣
በትምሕርተ ክርስቶስ ያላመኑትን አሳምኖ ያመኑትን ያጸና፣
ሽፍቶችን እየገሠጸ ለንስሐ ያበቃ የነበረ ታላቅ አባት ነው።

በዘመነ ሰማዕታት ስደትን ታግሦ በኋላም በደብረ ሲሐት ተወስኖ ኑሯል። በዚህች ቀንም በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።

አምላከ ቅዱሳን ፍቅሩን ምሥጢሩን ይግለጥልን። ከጾመ ገሃድ በረከትም አይለየን።

ጥር ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ጾመ ገሃድ
፪.አባ ታውብንስጦስ ዘሲሐት
፫.ቅዱስ ኪናርያ
፬.ቅድስት ጠምያኒ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፭.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
፮.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
፯.ቅዱስ እፀ መስቀል

"እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና። ልጅነትና ክብር፣ ኪዳንም፣ የሕግም መሰጠት፣ የመቅደስም ሥርዓት፣ የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና። አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና። ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ። እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው። አሜን።"
(ሮሜ ፱፥፬-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአበው ቅዱሳን አባ አብርሃም ወአባ ገዐርጊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን አብርሃም ወገዐርጊ <3

ቅዱሳኑን የመሰሉ አባቶች በግዕዙ "መስተጋድላን" ይባላሉ። ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው። መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው።

ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ። ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ። የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከሁለት አካላት ጋር ነው። በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖታችሁን ካዱ፤ ለጣዖትም ስገዱ።" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው።

በተለይ ሁለተኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል። የእነዚህን ቅዱሳን ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ።

ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ። ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ። ይኸውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል።

ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል። ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው። ፍቅረ መስቀሉን የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም።

ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኸው ነው። ጌታችን "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ።" (ማቴ. ፲፮፥፲፰) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን።

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው። በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል። ሕይወቱ በጐላ በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው።

ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል።

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለአርባ ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል፤ አስተምሯል። በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት።

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። አኗኗራቸውም በቡድንም በነጠላም ሊሆን ይችላል።

ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው። ይህም ሲያያዝ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደረሰ። በዚህ ዘመን ግን አባ ጳውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይህንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው። ለሰማንያ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ። ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ።

ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት። በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ። ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ።

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል። ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል።

አባ እንጦንስ አባ መቃርስን፣ አባ መቃርስ አባ ዮሐንስን ወልደዋል። አባ ዮሐንስም የታላቁ ገዳመ አስቄጥስ አበ ምኔት ሆነው በጸጋ አገልግለዋል። አስቄጥስ በምድረ ግብጽ የሚገኝ በስፋቱና ብዙ ቅዱሳንን በማፍራቱ ተወዳዳሪ የሌለው የዓለማችን ቁጥር አንድ ገዳም ነው።

ሕይወተ ምንኩሰናም ወደ መላው ዓለም የተስፋፋ በዚህ ገዳም መናንያን አማካኝነት ነው። በዚህ ገዳም ላይ የሚሾሙ አበው ደግሞ በብዛት መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸውና አባታቸውን ቅዱስ መቃርስ ታላቁን የመሰሉ ናቸውና ኃላፊነቱ እጅግ ከባድ ነው።

በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ተወልደው ያደጉት አባ ዮሐንስ ከመነኑባት ዕለት ጀምረው በፍጹም ተጸምዶና ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ስለ ተገዙ የታላቁ ገዳም አበ ምኔት ሊሆኑ ተገባቸው።

በአበ ምኔትነት ዘመናቸውም መንጋውን ይጠብቁ ዘንድ ብዙ ደከሙ። በተለይ ቅዱስ ቃሉን ያስተምሩ ዘንድ ተጉ። ሕይወተ መላእክትንም ያሳዩ ዘንድ በቃል ብቻ ያይደለ በተግባር ሆነው ከመንፈሳዊ አብራካቸው ብዙ ቅዱሳንን ወለዱ።

ከዋክብቱ አባ ገዐርጊ፣ አባ አብርሃም፣ አባ ሚናስ፣ አባ ዘካርያስ..... የአባ ዮሐንስ ፍሬዎች ናቸውና። ጻድቁ በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል። ከዕረፍታቸው በኋላ እንኳ መግነዛቸውና የልብሳቸው እራፊ ብዙ ድውያንን ፈውሷል።

ቅዱሳን አብርሃም ወገዐርጊ በግብጽ በርሃ ያበሩ የቅዱሱ አባ ዮሐንስ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቹ ናቸው። አስቀድሞ ወደ በርሃ የወጣ አባ አብርሃም ሲሆን እርሱም በምድረ ግብጽ የተባረኩ ሰዎች ልጅ ነው።

ወላጆቹ በፈቃደ እግዚአብሔር እርሱን ከወለዱ በኋላ ብዙ በጐነትን አሳይተዋል። ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የችግርና የረሃብ ጊዜ) ነበርና ሃብታቸውን በምጽዋት ጨርሰዋል። የሚገርመው የቅዱሱ አባት "ነዳያን እየተራቡ ዝም አልልም።" ብሎ እየተበደረ ያበላቸው ነበር።

እርሱ ባረፈ ጊዜም የተባረከች ሚስቱ መልካምን እየሠራች ብዙ ተፈትናለች። ለባርነት ተማርካ እስክትሔድ ድረስም ታግሣለች። ቅዱሱን ልጇን አብርሃምንም እንደሚገባ አሳድጋ "ሚስት ላጋባህ?" አለችው።

እርሱ ግን "እናቴ ሆይ! እኔ ይህንን ዓለም አልፈልገውም።" ሲል መለሰላት። ይህንን ስትሰማም ሐሴትን አድርጋ አብርሃምን ወደ በርሃ ሸኘችው። አባ አብርሃምም ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሔዶ በደብረ አባ መቃርስ መነኮሰ። ተጋድሎንም በዚያው ጀመረ።

ሲጾም፣ ሲጸልይ፣ ሲጋደልም ዘመናት አለፉ። በዚህ ጊዜም ታላቁ አባ ገዐርጊ ከዓለም ወደ በርሃ መጥቶ መነኮሰ። ከአባ ዮሐንስ የመንፈስ ልጆች ውስጥም እንደ አንዱ ተቆጠረ። አባ ገዐርጊን የተመለከተው አባ አብርሃምም ስለ ወደደው አብረው መኖር ጀመሩ።

ሁለቱ ቅዱሳንም "በግቢግ" በምትባል በዓታቸው በፍቅር ለፈጣሪያቸው ሲገዙ ዘመናት አለፉ። በእነዚህ ዘመናትም በርካታ ቅዱሳንን ከመንፈሳዊ አብራካቸው አፈሩ ከቅድስናቸው ብዛትም ከሰንበት በቀር እህልን አይቀምሱም ነበር።

የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ ቀን ከዓለት በተወቀረች በዓታቸው ውስጥ በጸሎት ላይ ሳሉ ወረደላቸው። የበዓታቸውን ዓለት ሰንጥቆ ሲገባ ታላቅ ግርማና ብርሃን አካባቢውን ዋጠው። ቅዱሳኑም ለመድኃኒታችን ተደፍተው ሰገዱ።

እርሱ አነጋግሯቸው፣ ባርኳቸው ዐርጓል። ለምልክትም በዓታቸው እንደ ተሰነጠቀ ቀርቷል። ዘወትርም በዕለተ ሰንበት ይገለጥላቸው ነበር። ቅዱሳን አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም በርካታ ተአምራትን ሲሠሩ ኑረዋል።

አባ አብርሃም ጥር ፱ ቀን ሲያርፉ አባ ገዐርጊ ግንቦት ፲፰ ቀን ዐርፎ ተቀብሯል። በዓታቸው በግቢግም ዛሬ ድረስ በምድረ ግብጽ አለች።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን አበው አባ መቃርስ እና ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ ቅዱስ መቃርስ <3

ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ፣ ከሰማንያ ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ፣ በግብጽ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ፣ ከሃምሳ ሺህ በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው።

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብጽ ወደ እስያ በርሃ ከጓደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል። በዚያ ለሁለት ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በኋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነ ንጉሳቸው አጥምቀዋል።

በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ አዕላፍ መላእክትን በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን፣ ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን፣ ማርቆስን፣ ጴጥሮስን፣ ጳውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል። በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።

ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከሁለት ዓመታት ስደትና መከራ በኋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልአኩ ኪሩብ በክንፉ ተሸክሞ ወደ ግብጽ መልሷቸዋል። በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከሃምሳ ሺህ በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል።

ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በኋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ። ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ ይባላሉ።) የኖሩባት ቦታ ናት። የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው።

በምድረ ግብጽ በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር። መስረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር አንድም ለበረከት አደረጉት።

ወደ ሳስዊርም ወስደው ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት። በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ። በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ። በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ። በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት።

በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ። አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት በነበረበት ዘመን ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ።

ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና። ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላችኋለን።" ብለው ሰይፍ፣ ዱላ፣ ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው።

መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ። መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራእይ ተቆጣው። በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ።

ሕዝቡም በዝማሬና በማኅሌት ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው። ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ። ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል።

ይህች ዕለት ቅዳሴ ቤቱ ስትሆን የተቀደሰችውም በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ብንያሚን እጅ ነው።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ እና ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሥሉስ ቅዱስ <3

ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም።

እግዚአብሔር አንድም ነው፤ ሦስትም ነው። ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነቱ፤ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው።

ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው። ዓለምን ከፈጠረ በኋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምህርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው።

ይኸውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው። ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርህ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም።

እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ።
እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው። ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ያውቃል።

በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት) በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘላለም አምላክ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው። አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነት በባሕርይ፣ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው። በዚህ ጊዜ ተገኙ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም። መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና።

ርኅሩኀን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን። የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም። የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል። በቤቱም መጥተው ያድራሉ።

ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም። አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል።

አባታችን አብርሃም በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ እናታችን ሣራ በሰማንያ ዘጠኝ ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ። አብርሃም እግራቸውን አጠበ። (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው። (ድንቅ አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው። እንደሚበሉ ሆኑለት። በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት።

ሥላሴን ያስተናገደች ድንኳን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት። በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል (አድረዋልና)።

በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ ሁለት ምክንያቶች ነው። ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው።

ሰናዖር ከሺህዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር። ከናምሩድ ክፋት በኋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ።

ከጥፋት ውኃ (ከኖኅ ዕረፍት) በኋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ። በዚያውም አባቶቻችን በውኃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው።" ተባባሉ።

ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ። ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በፀሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል። ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል።

መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል። ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው። ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን።

ርኅሩኀን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም። የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና። ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን - ቋንቋቸውን እንደባልቀው።" አሉ እንጂ።

ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ ሰባ አንድ ቋንቋዎች ተፈጠሩ። እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ። ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት። ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል።

ዳግመኛ በዚህች ዕለት አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮጵያ በነገሡ በአሥረኛው ዓመት (በ፲፮፻፹፬ ዓ/ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች።

ጥር ፯ ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን፣ ሠራዊት፣ መሳፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል። በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጓል። ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል፣ ደግ፣ ጥበበኛ፣ አስተዋይ፣ መናኝ ንጉሥ ነውና።

ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል። ነገር ግን በተሠራች በአሥራ ስድስት ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል። ዛሬ የምናየው በ፲፯፻፰ ዓ/ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ) <3

ቅዱሱ "ወንጌሉ ዘወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ከሌሎች "ዮሐንስ" ከሚባሉ ቅዱሳን ለመለየት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን እድሜ ልኩን የሚያነበው ከእጁ የማይለየውና አቅፎት የሚተኛ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል ስለ ነበረው ነው።

የቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩ በሆነ መንገድ ከመርዓዊ (ሙሽራው) ገብረ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ሙሴ ሮማዊ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በሮም ግዛት ሥር የሚኖሩ አጥራብዮስና ብዱራ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ። እግዚአብሔር በቀደሰው ትዳር የሚኖሩና ነዳያንን የሚዘከሩ ነበሩና ይህንን ቅዱስ ወለዱ። ስሙን ዮሐንስ ብለው እንደሚገባም አሳድገው ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያትን እንዲረዳ ለመምህር ሰጡት። ቅዱስ ዮሐንስ ከመምህሩ ዘንድ ቁጭ ብሎ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን ተማረ።

ለወላጆቹ ቅንና ታዛዥ ነበርና አባቱ "ልጄ! የምትፈልገውን ጠይቀኝ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለው። ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድሮ እኛን የሚያምረን ሁሉ አላሰኘውም። አባቱን "ቅዱስ ወንጌልን ግዛልኝ፤ በወርቅም አስለብጠው።" አለው። አባትም የተባለውን ፈጸመ።

ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እስካረፈባት ቀን ድረስ ቅዱስ ዮሐንስና የወርቅ ወንጌሉ ተለያይተው አያውቁም። ሁሌም ያለመታከት ያነበዋል። ሲቀመጥም ሲነሳም፣ ሲሔድም ሲተኛም አብሮት ነበር።

ቅዱስ ዮሐንስ ወጣት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይድሩት ዘንድ ተዘጋጁ። ልብሰ መርዐም (የሙሽራ ልብስ) አዘጋጁ። በዚያው ሰሞን ግን አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤታቸው መጥቶ ያድራል። በዚያች ሌሊት መነኮሱ በጨዋታ መካከል ስለ ቅዱሳን መነኮሳት ተጋድሎና ክብር ነገረው። የሰማው ነገር ልቡናውን የማረከው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደ ፈጣሪው ይለምን ነበር።

አንድ ቀን ግን ያ መነኮስ በድጋሚ መጥቶ አደረ። ቅዱስ ዮሐንስ መነኮሱን ወደ ገዳም እንዲወስደው ቢጠይቀው "አይሆንም፤ አባትህ ያዝንብኛል።" አለው። ቅዱሱ ግን "በእግዚአብሔር ስም አማጽኜሃለሁ።" ስላለው ሁለቱም በሌሊት ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ።

አበ ምኔቱ "ልጄ! የበርሃውን መከራ አትችለውም ይቅርብህ።" ቢለውም "አባቴ! አይድከሙ። ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር አይለየኝም፣'' ስላላቸው እንደሚገባ ፈትነው አመንኩሰውታል። ቅዱስ ዮሐንስ ከመነኮሰ በኋላ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና በትሕርምት ያሳየው ተጋድሎ በርካቶችን አስደነቀ።

ለሥጋው ቦታ አልሰጣትምና በወጣትነቱ አካሉ ረገፈ። ቆዳውና አካሉም ተገናኘ። ሥጋውን አድርቆ ነፍሱን አለመለማት። በእንዲህ ያለ ሕይወት ለሰባት ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በራእይ "ወደ ወላጆችህ ተመለስ።" እያለ ሦስት ጊዜ አናገረው።
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ አበ ምኔቱ ሔዶ ቢጠይቀው "ራእዩ ከእግዚአብሔር ነው።" ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አሰናበተው።

ቅዱስ ዮሐንስ በላዩ ላይ የነበረችውን ልብስ በመንገድ ለነዳይ ሰጥቶ በፈንታው ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ ከወላጆቹ በር ላይ ለመነ። "እባካችሁ አስጠጉኝ።" አላቸው። ወላጆቹ በጭራሽ ሊለዩት አልቻሉም። ነገር ግን አሳዝኗቸዋልና በበራቸው አካባቢ ትንሽ ቤት ሠሩለት።

በዚያች በዓት ውስጥ እንዳስለመደ በትጋት ለሰባት ዓመታት ተጋደለ። በእነዚህ ዓመታት እንኳን ሌላው ሰው ወላጆቹም ቢሆኑ ፍርፋሪ ከመስጠት በቀር አይቀርቡትም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ "ይሸተናል" የሚል ነበር። በመጨረሻም መልአከ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ "ከሰባት ቀናት በኋላ ታርፋለህ።" አለው።

እናቱን ጠርቶ "አንድ ነገር ልለምንሽ።" አላት። "እሺ" አለችው። "ከሞትኩ በኋላ በለበስኳት ጨርቅ እንድትገንዙኝ በበዓቴ ውስጥም እንድትቀብሩኝ።" አላትና የወርቅ ወንጌሉን አውጥቶ ሰጣት። ያን ጊዜ አባቱም ደርሶ ነበርና ደነገጡ።

የወርቅ ወንጌሉን ለዩት። ልጃቸውን ግን መለየት አልቻሉምና እያለቀሱ ስለ ልጃቸው የሚያውቀው ካለ እንዲነግራቸው ለመኑት። እርሱም "ልጃችሁ ዮሐንስ እኔ ነኝ።" አላቸው።

በዚያች ቅጽበት ወላጆቹ የሰሙትን ማመን አልቻሉም። በፍጹም ዋይታ እየጮሁ አለቀሱ። ለቅሷቸውን የሰሙ ሁሉ ተሰበሰቡ። ለሰባት ቀናት እኩሉ እያለቀሰ እኩሉ እየተባረከ በዓቱን ከበው ሰነበቱ። በሰባተኛው ቀን መልአኩ መጥቶ በክብር ነፍሱን ተቀበለ።

እናቱ የልጇን አደራ ረስታ (እሷስ መልካም አደረግሁ ብላ ነው።) ለሠርጉ ባዘጋጀችው የወርቅ ልብስ ገነዘችው። ወዲያው ግን በጽኑ ታመመች። አባት ግን ፈጠን ብሎ በዚያች ጨርቅ ገንዞ በበዓቱ ውስጥ ቀበረው። ያን ጊዜ እናት ፈጥና ዳነች። ከቅዱሱ መቃብርም ብዙ ተአምራትና ፈውስ ተደርጓል።

ቸሩ እግዚአብሔር ከወዳጆቹ በረከት ያሳትፈን።

ጥር ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ (ሰማዕትና ጻድቅ)
፪.ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
፫.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ (ቅዳሴ ቤቱ)
፬.አባ አብድዩ ጻድቅ
፭.ቅዱስ ብሕኑ ሰማዕት
፮.ቅዱስ አብሮኮሮስ ሐዋርያ (የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር)
፯.አባ ኖኅ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፪.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት
፫.ቅዱስ አሞንዮስ
፬.ቅዱስ ካሌብ ንጉሠ ኢትዮጵያ
፭.ቅድስት ሳድዥ የዋሂት

"እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ። በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሱ።
የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ። እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ። በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ።"
(ኤፌ ፮፥፲፬-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን <3

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን (በተለይ ከአሥራ ሦስተኛው እስከ አሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ያለው) የብርሃን ዘመን ይባላል።
ምክንያቱም ዘመኑ፦
ክርስትና ያበበበት፣
መጻሕፍት የተደረሱበት፣
ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት፣
ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው።

ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ
አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣
አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣
አባ ሰላማ ካልዕ፣
አቡነ ያዕቆብ፣
ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ፣
አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅና አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው።

በተጨማሪም፦
አሥራ ሁለቱ ንቡራነ ዕድ፣
ሰባቱ ከዋክብት፣
አርባ ሰባቱ ከዋክብትና አምስቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር።
ከእነዚህ መካከልም የሰባቱ እና የአርባ ሰባቱ ከዋክብት አስተማሪ፣ የአበው ሦስቱ ሳሙኤሎች (ዘዋልድባ፣ ዘጣሬጣና ዘቆየጻ)ና የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ።

ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው፣ አስተምረው፣ አመንኩሰው፣ መርቀው ሰደው ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ።

ከእነዚህ ቅዱሳን የጻድቁ ፍሬዎች አንዱ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ናቸው። ጻድቁ አንዳንዴ "አፍቀረነ እግዚእ" እየተባሉም ይጠራሉ። ትርጉሙም "ጌታ ወደደን።" እንደ ማለት ነው።

ያፍቅረነ እግዚእ የነበሩት በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን ቁጥራቸው ከሰባቱ ከዋክብት ነው። ጻድቁ ከልጅነት ጀምሮ በሥርዓቱ ከማደጋቸው ባሻገር እጅግ የተማሩ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል።

ለምናኔ ከወጡ በኋላ ከኖሩባቸው ቦታዎችም ሦስቱ ተጠቃሽ ናቸው። የመጀመሪያውና ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ደግሞ ደብረ በንኮል ነው። ጻድቁ በዚህ ገዳም ከታላቁ ቅዱስ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሥርዓተ ገዳምን፣ ትሕርምተ አበውን፣ ተጋድሎተ ቅዱሳንን አጥንተው ለመዓርገ ምንኩስና በቅተዋል።

በገዳሙም ለተወሰነ ጊዜ አገልግለው ወደ ጣና አካባቢ ከአቡነ ያሳይና ከአባ ሳሙኤል ዘዋሊ ጋር መጥተዋል። የመምጣታቸው ምክንያትም ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስና ገዳማትን ለመመሥረት ነው።

ሦስቱ ቅዱሳን ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ ደግሞ ማንዳባን አቀኑ። ያፍቅረነ እግዚእም ጌታ ባዘዛቸው መሠረት ጣና ውስጥ ገዳም አቅንተው ኑረዋል። ይህ ገዳማቸው ዛሬም ድረስ በስማቸው ይጠራል።

ጻድቁ አፍቀረነ እግዚእ ሦስተኛው የሚታወቁበት ገዳም ማኅበረ ዴጌ (ጻድቃነ ዴጌ) ሲሆን ገዳሙ በአክሱም ዙሪያ ይገኛል። እርሳቸው ሦስት ሺህ ቅዱሳን የተሠወሩበትን ገዳም በማገልገላቸውም ዛሬም ድረስ በአካባቢው የታወቁ ሆነዋል።

በተረፈም አክሱም አካባቢ ሌሎች ገዳማትን እንዳቀኑም ይነገርላቸዋል። ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ለብዙ ዘመናት በተጋድሎ፣ በስብከተ ወንጌልና ገዳማትን በማስፋፋት ከኖሩ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፈው ለክብሩ፣ ለርስቱ በቅተዋል።

አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ አማላጅነት ይቅር ብሎ በረከታቸውን ያሳድርብን።

ቅዱሳንን ታስቡ ዘንድ ቸል አትበሉ።

ጥር ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ (አፍቀረነ እግዚእ ዘጉጉቤ ጣና ውስጥ ከሰባቱ ከዋክብት አንዱ)
፪.አባ ባሱራ
፫.ቅድስት ኔራ
፬.ቅድስት በርስጢና
፭.አባ ዝሑራ
፮.አባ ጽሕማ (ከተስዓቱ ቅዱሳን አንዱ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫.አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ታቦታቸው ጎንደር ከተማ ቀበሌ ፱ አካባቢ ይገኛል።)
፬.አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና።
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል።.....
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ጥር ፲፰፦ ዝርዎተ አጽሙ ለሊቀ ሰማዕታት ማር ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዳግመኛም ያ ከሃዲ ንጉሥ ዱድያኖስ ግንድ አምጥተው ቅዱስ ጊዮርጊስን በግንዱ ላይ እንዲቸነክሩት አዘዘ። በላዩም ላይ ሰም አፍስሰው እሳት እንዲያነዱበት አደረገ። ከዚህም በኋላ እንደመጭመቂያ ሆኖ ከተሠራ የስቃይ መሣሪያ ላይ አወጡት፤ ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት እንዲጨምቁት አዘዘ። አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረገፍ ድረስ እንዲሁ አደረጉበት፤ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። የሰማዕቱን ሥጋ አቃጠሉት ፈጩት አመድም ሆነ በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ላይ በነፋስ ዘሩት። ደብረ ይድራስ ማለት ምድረ በዳ ነው፤ ወታደሮቹ የታዘዙትን ፈጽመው ተመለሱ። ያንጊዜም መብረቅ ነጎድጓድ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ፤ ምድርም ከመሠረቷ እስክትናወጽ ድረስ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መላእክትን አስከትሎ በብሩህ ደመና ወረደ፤ በተራራውም ላይ ተቀመጠ። አራቱን የምድር ነፋሳት የሰማዕቱን ሥጋ እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው፤ ከሞትም አስነሳው ኃይሉን አሳደረበት ባርኮትም ወደ ሰማይ አረገ። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየሮጠ ወታደሮቹን ተከተላቸው፤ ወንድሞቼ ቆዩኝ ከእናንተ ጋር ልሒድ እያለ ተጣራ። የእነዚህ የወታደሮች ቁጥር አራት ነው። ስማቸው ህልቶን፣ አግሎሲስ፣ ሶሪስና አስፎሪስ ነው። ይህንን ታላቅ ተአምራት አይተው አምነዋል፤ በኋላም በሰማዕትነት ሞተዋል። ይህ የሆነው ጥር ፲፰ በዛሬዋ ቀን ነው። ይህንንም ቀን "ዝርዎተ አጽሙ" ስትል ቤተ ክርስቲያን ሰማዕቱን አዘክራ ትውላለች።
<3 ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን። <3

ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምዕራፍ ፮፥፲፭-፲፰

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቅዱስ ባኮስ፣ ቅዱስ ያዕቆብ እና ደናግል ማርያ ወማርታ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ <3

መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰባት ዓመታት ስቃይ በኋላ ተሰይፏል።
ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ፦
ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃያ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሥልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው። እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ፣ አሳምኖ፣ ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ሰባ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር። በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው። እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ።

ከዚያም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ። ሦስት ጊዜ ሙቶ ተነሳ። ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው፣ ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል።
"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ።" እንዲል መጽሐፍ።

ከሰባት ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም፣ ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል። ሰባት አክሊላትም ወርደውለታል።

ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ "ዝርወተ አጽሙ" ትባላለች። በቁሙ "አጥንቱ የተበተነበት" እንደ ማለት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው። ሰባ ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ።

በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ። ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት። ያለ ርኅራኄም አካሉን አሳረሩት። ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት።

በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት።
"ሐረድዎ ወገመድዎ ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል።
(ምቅናይ)

እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች፣ ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ። ስለዚህም ይህቺ ዕለት ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው።

ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው። ሰባው ነገሥታት ግን አፈሩ።

<3 ቅዱስ ባኮስ ጃንደረባው <3

"ጃንደረባ" የሚለው ቃል በግዕዙ "ሕጽው" ተብሏል። ይህ ስም በቤተ ክርስቲያን የተለመደ እንጂ እንግዳ አይደለም። መድኃኒታችን እንዳለው በተፈጥሮ የሆኑ፣ ሰዎች እንዲያ ያደረጓቸውና ራሳቸውን ስለ ጽድቅ ጃንደረባ ያደረጉ ብዙዎች ናቸውና።

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ቅዱስ ባኮስም (አንዳንዴ አቤላክ/አቤሜሌክም ይባላል።)
በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሃገራችን ኢትዮጵያ ተወልዶ ያደገ፣
ነገሥታቱንና ሃገሩን በሙያው ያገለገለ፣
በተለይ ከ፴፬ - ፵፮ ዓ.ም ለነገሠችው ንግሥት ሕንደኬ ገርስሞት በገንዘብ ሚንስትርነት ያገለገለ፣
በገንዘቧ ላይ ሁሉ አዛዥ (ታማኝ) የነበረ፣
ጃንደረባ በመሆኑ ለንግሥቲቱና ቤተሰቧ ቅርብ የነበረ፣
መጻሕፍትን የሚያነብና የሚመረምር፣
ዘወትር ወደ ኢየሩሳሌም እየሔደ ከቅዱሳት መካናት የሚሳለም በጐ ሰው ነበር።

በግብረ ሐዋርያት ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፳፯ ላይ እንደ ተጠቀሰው ቅዱሱ ወደ ኢየሩሳሌም የሔደው ለፋሲካና ለእሸት በዓል ነበር። ሲመለስ መንፈስ ቅዱስ ከፊልጶስ ጋር በጋዛ አገናኝቶታል። በዚያም ምሥጢረ ክርስትናን ተምሮ በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት አምኖ ተጠምቋል።

ክርስትናን ለኢትዮጵያ በ፴፬ ዓ.ም አምጥቷል። "ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ።" ሲል ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንደ ተናገረው ወደ ሃገራችን ተመልሶ ስለ ክርስቶስ ሰብኮ በርካቶችን አሳምኗል።

ቀጥሎም ሃብቱን ንቆ (መንኖ) ከኢትዮጵያ እስከ ሕንድ ወንጌልን ሰብኮ በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ዐርፏል። (ተሰውሯል የሚሉም አሉ።)
በእውነት ለቅዱስ ባኮስ ክብር ይገባል!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ወክቡራን ጻድቃን መክሲሞስ ወዱማቴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አበዊነ መክሲሞስ ወዱማቴዎስ <3

እነዚህ ቅዱሳን የሥጋ ወንድማማቾች ሲሆኑ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እጅግ ተወዳጅ አባቶች ናቸው። ስንጠራቸውም "አበዊነ ቅዱሳን፣ ወክቡራን፣ ሮማውያን፣ መስተጋድላን ወከዋክብት ብሩሃን" ብለን ነው።

ይኸውም "እንደ ንጋት ኮከብ የምታበሩ፣ ተጋዳይ፣ ቅዱሳንና ክቡራን የሆናችሁ ሮማውያን አባቶቻችን" ማለት ነው። ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ሁና አባታቸው ንጉሥ ለውንድዮስ ይባላል።

ይህ ንጉሥ ሮምን በምታክል ታላቅ ሃገር በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነግሦ ሳለ መልካም ሰው ሆኖ ተገኝቷል። ከመልካም ሚስቱ (ንግሥቲቱ) ከወለዳቸው መካከልም ሁለቱ ከዋክብት ይጠቀሳሉ። ሁለቱ ቅዱሳን በአጭር የጊዜ ልዩነት የተወለዱ በመሆናቸው እንደ መንትያ ይቆጠራሉ።

ንጉሡ ለውንድዮስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ላገኛቸው ልጆቹ ስም ሲያወጣ ታላቁን መክሲሞስ ታናሹን ደግሞ ዱማቴዎስ ብሎታል። ቅዱሳኑ በንጉሥ አባታቸው መልካም ፈቃድ ክርስትናን ተምረዋል።

ምንም እንኳ የንጉሥ ልጆች እና ልዑላን ቢሆኑም ተቀማጥለው አላደጉም። ምቾት ብዙዎችን አጥፍቷልና። ይህንን የተረዳ አባታቸው ሞገስን በፈጣሪያቸው ዘንድ እንዲያገኙ እንዲህ በበጐ ጐዳና አሳደጋቸው።

ቅዱሳን መክሲሞስና ዱማቴዎስ ካደጉና ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ ይተጉ ነበር። በተለይ ዜና ቅዱሳንን ከማንበብ አይጠግቡም ነበር። እግዚአብሔርንም በፍቅር እያመለኩ በጾምና በጸሎት ይገዙለት ነበር።

ቅዱሳኑንም ለየት የሚያደርጋቸው አንዱ ይሔው ነው። ወርቅና ብር በፊታቸው ፈሶ በእግራቸው እየረገጡት፣ አገሩና ምድሩ እየሰገደላቸው፣ የላመ የጣመ ምግብ እየቀረበላቸው፣ የሞቀ የደመቀ መኝታ እየተነጠፈላቸው ሁሉንም ስለ ፍቅረ ክርስቶስ መናቃቸው ይደነቃል።

እነርሱ በክርስቶስ ፍቅር ሆነው የዚህን ዓለም ጣዕም ንቀዋልና የአባታቸውን ቤተ መንግሥት ሊተዉ አሰቡ። አሳባቸው ደግሞ በመመካከር ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት "እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ" እንዲሉ አበው በጌታ መሪነት ነው።

ወደ በርሃ ሔደው ለፈጣሪ ለመገዛት ሲያስቡ መውጫ መንገዳቸውን ይሹ ነበርና አንድ ጐዳና ተገለጠላቸው። ከዚያም ለንጉሥ አባታቸው ሔደው "አባ! እኛ ወደ ኒቅያ (ታናሽ እስያ) ሔደን መባረክ እንፈልጋለን።" ሲሉ ጠየቁት።

ወቅቱ ቦታዋ ስለ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ሞገስን ያገኘችበት ጊዜ ነበር። አባታቸውም መንፈሳዊ ሰው ነበርና ደስ እያለው ፈቀደላቸው። ብዙ ወርቅን ሰጥቶ ሸልሞ ከብዙ ሠራዊት ጋር ሸኛቸው።

ቅዱሳኑ መክሲሞስና ዱማቴዎስም ለጥቂት ጊዜ በኒቅያ ሲጸልዩና ሲባረኩ ሰነበቱ። ቀጥለውም የአባታቸውን ሰራዊት ሰብስበው "እኛ ሱባኤ ልንይዝ ስለ ሆነ እንመጣለን።" የሚል ደብዳቤን ሰጥተው ወደ ሮም ሸኟቸው።

ወታደሮችን ከሸኙ በኋላ ቅዱሳኑ በአካባቢው ወደ ሚገኝ አንድ ገዳም ሒደው ለአንድ ደግ መናኝ ምሥጢራቸውን ገለጹለት። ልክ የንጉሡ ለውንድዮስ ልጆች መሆናቸውን ሲያውቅ "አመንኩሰን" ያሉትን እንቢ አላቸው።

"ለምን?" ሲሉት "ደጉን አባታችሁን ማሳዘን አልፈልግም። ግን ፈቃዳችሁ እንዲፈጸምላችሁ ወደ ሶርያ ዝለቁ። በዚያ አባ አጋብዮስ የሚባል ጻድቅ ገዳማዊ ሰው ታገኛላችሁ።" ብሎ ወደ ሶርያ አሰናበታቸው።

በምድረ ሮም በተለይም በቤተ መንግሥቱ አካባቢ የሁለቱ ልዑላን መጥፋት (መሰወር) ሲሰማ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ። ንጉሡ አባታቸው በወታደሮቹ ዓለምን ቢያካልልም ሊያገኛቸው አልቻለም። እርሱ ፈጽሞ ሲያዝን እናታቸው ፈጽማ መጽናናትን እንቢ አለች።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአበው ቅዱሳን አባ ዳንኤል፣ አባ ጰላድዮስ ወቅዱስ ፊላታዎስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ማር ዳንኤል <3

"ዘዓምድ" በሚል ስም ከሚታወቁ የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል አራቱ ቅድሚያውን ይይዛሉ።
እነዚህም፦
፩.ቅዱስ ስምዖን ዘዓምድ
፪.ቅዱስ አጋቶን ዘዓምድ
፫.ቅዱስ ዳንኤል ዘዓምድ እና
፬.ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ ናቸው።

"ዘዓምድ" የሚለውን ቃል ምሥራቃውያን በልሳናቸው 'THE STYLITE' ይሉታል። የእኛው ቃል ደግሞ ከግዕዝ የተወረሰ ነውና በቁሙ ቢተረጐም "የምሰሶው" የሚል ትርጉምን ይይዛል። ይህም በሁለት ምክንያቶች ነው።

አንደኛው ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን የፈጸሙት ከረዥም ምሰሶ ላይ ወጥተው በመጸለይ ስለሆነ ነው። ሌላኛው ምክንያት ደግሞ እነዚህ አባቶች በዘመኑ ለነበሩ ምዕመናንና መነኮሳት አጽናኝ፣ አስተማሪ፣ መሪና ፈዋሽ በመሆናቸውና እንደ ምሰሶ ተተክለው ሳይነቃነቁ በመጸለያቸው ነው።

ልክ ከዓለም ሃገራት ብዙ ስውራንን እና ቅዱሳን ነገሥታትን በመያዝ ሃገራችን ቀዳሚ እንደ ሆነችው ሁሉ ምሰሶ ላይ ወጥተው የሚጋደሉ ቅዱሳንም ሶርያውያንና ምሥራቃውያን ናቸው። በዚህ ዕለትም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የታላቁን ቅዱስ ማር ዳንኤልን በዓል ታከብራለችና ከዜና ሕይወቱ ለበረከት ጥቂት እንካፈል።

ይህ ቅዱስ ሰው ሶርያዊ ሲሆን ተወልዶ ያደገባት አካባቢ በቀድሞው አጠራር "ሃገረ ዓምድ" ይሏታል።
"ማር" የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን ቅድስናንና አለቅነትን የሚገልጽ ስም ነው። በዚህ ስም ጥቂቶች ብቻ ሲጠሩበት ለሊቃውንትም፣ ለሰማዕታትም፣ ለጻድቃንም አገልግሏል።

ቅዱሱ "ማር" ብቻ ሳይሆን "ዘዓምድ" ተብሎም ተጠርቷል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እርሱም በፊት እንደ ጠቀስናቸው አበው ምሰሶ ላይ ተጠግቶ (ቆሞ) ትኩል ከመ ዓምድ ሆኖ በመጸለዩ ነው።

ማር ዳንኤል በምድረ ሶርያ ስመ ጥር ጻድቅ ነው። በዘመነ ጻድቃን መጨረሻ አካባቢ ከክርስቲያን ወገኖቹ ተወልዶ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድጐ ገና በልጅነቱ ለቤተ እግዚአብሔር ተሰጥቷል።

የወቅቱ የሃገረ ዓምድ ጳጳስ (አባ ጴጥሮስ) ለማር ዳንኤል ፍኖተ ጽድቅን (የሕይወት - የእውነትን ጐዳና) በማሳየት ከፍ ያለውን አስተዋጽኦ አበርክቷል። አስተምሮም ለመዓርገ ክህነት አብቅቶታል።

ቅዱሱ በእድሜው እየበሰለ ሲሔድ ግን ምርጫው ምናኔ ሆኖ በመገኘቱ በፈቃዱ ወደ በርሃ ሔደ። በዚያም መዓርገ ምንኩስናን ተቀብሎ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት ይጋደል ገባ።

ማር ዳንኤል በበዓቱ ተወስኖ ሲጾም፣ ሲጸልይና እግዚአብሔርን ሲያመልክ ከጸጋ (ከብቅዓት) ደረሰ። ብዙ ተአምራትንም በመሥራቱ ስም አጠራሩ በአካባቢው ተሰማ። እርሱ ግን ከሰው ይልቁንም ከሴቶች ይርቅ ላለማየትም ራሱን ይከለክል ነበር።

ለአንድ መናኝ በሰዎች መካከል ይልቁንም በተቃራኒ ጾታ ጐን መኖር ያልተፈቀደ ፈታኝም ድርጊት ነውና ከፈጣሪው ጋር እንዲህ የሚል ቃልን ገባ። "ከዚህ በኋላ ሴት ልጅን አላይም።" አለ። በእንዲህ ያለ የቅድስና ሕይወት ሳለ ወላጅ እናቱ ልታየው ተመኘች።

ወደ ገዳሙ መጥታም "ልጄ! ላይህ ሽቻለውና ልግባ ወይ ብቅ በል።" ስትል ላከችበት። ቅዱሱ ግን "እናቴ! ሴትን አላይም ብየ ቃል ስለ ገባሁ አልችልም።" ሲል መለሰላት። በጣም አዝና "እኔ ወልጄ፣ አዝዬ፣ አጥብቼ፣ አሳድጌ እንደ ሌሎች ሴቶች አስመሰልከኝ? በል ሁለት ሴቶች በአንድ ልብስ ሆነው ይዩህ!" ብላ ረግማው ወደ ቤቷ ተመለሰች።

የሚገርመው ማር ዳንኤል በበርሃ የበቃውን ያህል እናቱ በዓለም ሳለች በጐ ሰርታለችና እርሷም ጸጋውን አብዝቶላታል። በምን ይታወቃል ቢሉ ያቺ የተናገረቻት ነገር ሁሉ ደርሶበታልና።

አንድ ቀን ለገንዘብ ሲል አንድ ሰው የገደለውን አምጥቶ በቅዱሱ በር ላይ ጣለው። ቅዱሱም ያለ አበሳው ታሥሮ ወደ ከተማ ሲወሰድ መታጠቢያ (shower) ቤት ውስጥ የነበሩ ሴቶች ሊያዩት ቸኩለው አንድ ልብስ ለብሰው ወጥተዋል። ማር ዳንኤል ይህንን ሲያይ የእናቱ ነገር ትዝ ብሎት ሳቅ ብሏል።

በታሠረበት ቦታ ግን የሞተውን ሰው በጸሎቱ በማስነሳቱ በክብር ወደ በዓቱ ተመልሷል። የከተማዋ ንጉሥም ገዳምን አንጾለታል። በተረፈ ዘመኑም ለብዙ ቅዱሳን አባት ሆኖ እስከ እርጅናው አገልግሏል። በዚህች ቀንም በክብር ዐርፏል።

<3 አባ ጰላድዮስ <3

አባ ጰላድዮስም በተመሳሳይ የዘመነ ጻድቃን ፍሬ ነው። በርሃ ከገባባት ቀን ጀምሮ ጾምን፣ ጸሎትን አዘውትሮ ክርስትናውን አጽንቷል። ሙሉ እድሜውን በጐ በመሥራት በማሳለፉ ፈጣሪውን ሲያስደስት ለብዙዎች አንባ መጠጊያ መሆን ችሏል።

በጸሎቱ አካባቢውን በደኅንነት ይጠብቅ ነበር። ምዕመናን እንኳን ወደ እርሱ መጥተው ተባርከው ባሉበት ቦታ ሁነው ተማጽነው እንኳ መሻታቸውን አያጡም ነበር። ምንም ያህል ኃጢአተኞች ይሁኑ እግዚአብሔር ስለ አባ ጰላድዮስ ሲል ይለመናቸው ነበር።

አንድ ቀን አንድ ነጋዴ ሰው በባሕር ላይ ሲሔድ ድንገት ማዕበል ይነሳበታል። ብቻውን ነበርና ጨነቀው። እርሱ ያለባት ጀልባም ትንሽ በመሆኗ ልትሠበር ደረሰች። መዳን እንደ ማይችል ሲያውቅ ተስፋ ቆረጠ።

ድንገት ግን አባ ጰላድዮስ ትዝ ብሎት ቀና ብሎ "ጌታዬ! ስለ ቅዱሱ አባት ብለህ ብትምረኝ ለወዳጅህ መቶ ዲናር ወርቅ እሰጣለሁ።" ሲል ተሳለ። ቃሉን ተናግሮ ሳይጨርስ አባ ጰላድዮስ በጀልባው ላይ ቁጭ ብሎ ታየው። ማዕበሉም ጸጥ እንዲል አድርጐ ከወደብ አድርሶ ተለየው።

ነጋዴውም ፈጣሪውን ስለ ድኅነቱ እያመሰገነ መቶ ዲናር ወርቁን ይዞ አባ ጰላድዮስን ፍለጋ ወጣ። የሚያውቀው በዝና ብቻ ነበርና። መንገድ ላይም ሞሪት የሚባል መሪ አግኝቶ ከአባ ጰላድዮስ በዓት ደረሰ።

ከቅዱሱ ተባርኮ ወርቁን ቢያቀርብለት "ልጄ! እኔ ይህን አልፈልገውም። ለነዳያን በትነው።" አለው። ነጋዴው ሲወጣ ግን ሞሪት (መሪው) ገንዘቡን ፈልጐ ገደለውና ከጻድቁ በር ላይ ጣለው። ሃገረ ገዢውም ሲሰማ አባ ጰላድዮስን አሠረው።

ጻድቁ ግን የሞተውን ባርኮ አስነሳውና "ማን ገደለህ?" ቢለው "ሞሪት" ሲል መልሷል። መኮንኑ ሞሪትን ሊገድለው ቢልም "የለም" ብሎ ነጋዴውን በደስታ ሞሪትን ደግሞ በንስሐ ሸኝቷቸዋል። አባ ጰላድዮስ ግን ተረፈ ዘመኑን በቅድስና ሲጋደል ኑሮ በክብር ዐርፏል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አባ አርከሌድስ <3

በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን በግብጽም በሃገራችንም አሉ። ዋናውና በብዙ መጻሕፍት ዜናቸው የተጻፈላቸው ግን ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው። አባ አርከሌድስ የነበሩት በዘመነ ጻድቃን ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ናት።

ወላጆቻቸው ክርስቲያን በዚያውም ላይ ባለ ጠጐች ነበሩ። አባታቸው ደግሞ መስፍነ ሃገር ነበር። ቅዱሱን ወልደው በሕግ በሥርዓት አሳድገዋል። አባ አርከሌድስ ለአካለ መጠን ሲደርሱ ግን አባታቸው ሞተ።

መዋዕለ ሐዘናቸው ከተፈጸመ በኋላም እናት አባ አርከሌድስን ጠርታ "ልጄ! ሒድና የአባትህን ሹመት እጅ አድርግ።" አለችው። ለመንገድ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሰናድታ አገልጋዮችንና ብዙ ወርቅ (ለሿሚው አካል የሚሰጥ) ጨምራም ልጇን ሸኘችው።

ቅዱስ አርከሌድስም ከእናታቸው ተለይተው በአገልጋዮች ተከበው ወደ መርከብ ገቡ። በባሕር መካከል ሳሉ ግን ታላቅ ማዕበል ተነስቶ መርከቡን በታተነው። በመርከቡ የነበረው ሰው ሁሉ ሲያልቅ አባ አርከሌድስ ግን በስባሪ ላይ ተንጠልጥለው ተረፉ።

ዋኝተው ወጥተው ወደ ዳርቻ ሲደርሱም ማዕበል የተፋው አንድ በድን ወድቆ ተመልክተው ፈጸመው አለቀሱ። ወዲያውም በልባቸው የዚህን ዓለም ኃላፊነት አሰቡ። ሹመት ፍለጋ መሔዳቸውን ትተው ወደ ገዳም ሔዱ።

ወደ ምድረ ሶርያ ደርሰው በታላቁ ደብረ ሮማኖስ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበሉ። በእጃቸው የነበረውን ሁለት መቶ ዲናር ወርቅም ለገዳሙ አበረከቱ። ለጥቂት ጊዜ በገዳሙ ካገለገሉ በኋላም ጾማዕት (በዓት) ተሰጣቸው።

በዚህ ጊዜም "እንግዲህ ወደ ዓለም አልወጣም። የሴቶችን መልክም አልመለከትም።" ሲሉ ቃል ገቡ። በተጋድሏቸውም በጾም፣ በጸሎትና በትጋሃ ሌሊት ለአሥራ ሁለት ዓመታት ቀጠሉ። ጾማቸውም ሰባት ቀን ነበር። አምላክ ጸጋውን ስላበዛላቸውም ብዙ ድውያንን ፈወሱ።

ዜናቸውም እስከ ምድረ ሮሜ ተሰማ። እናታቸው (ሰንደሊቃ) የመርከቡን ዜና ከሰማች በኋላ የሞቱ መስሏት አልቅሳ ቤቷን የእንግዳ ቤት አድርጋ በበጎ ምግባር ትኖር ነበርና አንድ ቀን የልጇን ዜና ሕይወት ሰማች።

ከደስታዋ የተነሳ ፈጥና ወደ ደብረ ሮማኖስ ደርሳ "ልጄን ልይ።" አለች። ግን "ሴትን አላይም።" ብለው አባ አርከሌድስ ቃል ገብተዋልና ምን ይሁን! ሰንደሊቃም "አራዊት ይብሉኝ እንጂ ልጄን ሳላይ አልሔድም።" አለች። ወዲያው ግን "አባ አርከሌድስ ፈቅደዋልና ግቢ።" የሚል መልእክት መጥቶላት ገባች።

ግን ያገኘችው የጻድቁን ልጇን ሥጋ ነበር። ምክንያቱም የፈጣሪንም፣ የእናታቸውንም ልብ ላለማሳዘን እንዲወስዳቸው ለምነውት ዐርፈው ነበር። እናትም በልጇ ሥጋ ላይ እያለቀሰች እዚያው ዐረፈች። "አብራችሁ ቅበሩን።" የሚል ቃል ከቅዱሱ ሥጋ ስለ ተሰማም አብረው ቀብረዋቸዋል።

አምላከ ቅዱሳን ለእነርሱ ካደለው ፍቅራቸው ለእኛም አይንሳን። በረከታቸውንም ያብዛልን።

ጥር ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ አባ መክሲሞስ
፫.ቅዱስ አባ አርከሌድስ
፬.ቅድስት እምራይስ
፭.ቅድስት ምሕራኤል
፮.አራት ሺህ ሠላሳ አራት ሰማዕታት (ማኅበራነ ቅዱስ ቂርቆስ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ ስምዖን
፪.አባ ዮሐንስ
፫.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ (ሙሽራው)
፬.ቅዱስ ሙሴ
፭.ቅዱስ ፊልጶስ (ከሰባ ሁለቱ አርድዕት)
፮.ቅድስት ነሣሒት

"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና። ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል።.....
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱሳን ሰባቱ ደቂቅ <3

እነዚህ ሰባት ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው። ሰባቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል። ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል። የተቀጠሩትም የቤተ መንግሥቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው።

በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም፣ ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር። እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር፣ በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ።

ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ። አዋጅም አስነገረ። አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ ለጣዖትም ያልሰገደ ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ፣ እጅ እግሩ ለእስር፣ ደረቱ ለጦር፣ አንገቱ ለሰይፍ፣ ቤቱም ለእሳት ይሰጣል።" የሚል ነበር። በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ።

የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ። ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች። የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ ሰባቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ። ንጉሡ እነርሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ።" አላቸው። እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት።

ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል። ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው። ከቀናት በኋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ። ግን አልተሳካለትም። በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ዳኬዎስ ወጣ።

ከመውጣቱ በፊት ግን ሰባቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻችኋለሁ። ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ። ካልሆነ ሞት ይጠብቃችኋል።" ብሏቸው ነበር የወጣው። ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ። ውሳኔንም አስተላለፉ።

ዓለምን ንቀው ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ። አንድ ወታደር (በጐች አሉት።) ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ። ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር። ከእነርሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር።

አንድ ቀን ግን ከእነርሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ። ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው። ከዚያች ቀን በኋላ ሰባቱም አልወጡም። በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ። ከዚያች ቀን በኋላ ግን አልነቁም።

ያ የበጐች ባለቤት (ወታደር) ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል" ብሎ አዘነ። በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና። እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው።
ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው። እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም። ቀናት፣ ወራት፣ ዓመታት ተዋልደው ለሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት ተኙ።

አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ። በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው። እድሜአቸው ግን አራት መቶ ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር። ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ። ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት። ከተማዋ ዘምናለች።

በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ መስቀልም በየአደባባዩ ተተክለዋል። ነገሩ ግር ቢለው አንዱን ከመንገድ ጠርቶ "ወንድሜ! ይህች ከተማ ኤፌሶን አይደለችምን?" አለው። እርሱም "አዎ ናት።" ብሎት አለፈ።

ችግሩ ግን "ራት ልግዛ።" ብሎ ወደ ገበያ ሲሔድ እርሱ የያዘው ገንዘብ የዳኬዎስ ስም የተጻፈበት መሆኑ የፈጠረው ነበር። በነጋዴዎቹ "የተደበቀ የጥንት ገንዘብ አግኝተሃል።" በሚል ተከሶም ወደ ንጉሡ ቴዎዶስዮስ ዘንድ ቀረበ። (ትንሹ ቴዎዶስዮስ ነው። የነገሠውም በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው።)

በክርክሩ መካከል ቅዱሱ የእርሱንና የወንድሞቹን ነገር ሲናገር ንጉሡም፣ ሊቀ ጳጳሱም (አባ ቴዎድሮስ ይባላል።) ተገረሙ። አብረው ከከተማ ወጥተው ቢሔዱ ሲጸልዩ አገኟቸው። ፊታቸውም እንደ እግረ ፀሐይ ያበራ ነበር። ሰባቱም ለሰባት ቀናት በኤፌሶን ድውያንን እየፈወሱ ሰውን ሁሉ እየባረኩ ቆዩ።

ይህ ሁሉ የተደረገው በወቅቱ "ትንሣኤ ሙታን የለም።" የሚሉ መናፍቃን ተነስተው ብዙ ሰው ክዶ ነበርና ለእነርሱ ምሥክር ሊሆኑባቸው ነው። በርካቶችም በዚህ ድንቅ ተስበው ወደ ሃይማኖት ተመልሰዋል። ሰባቱ ቅዱሳን ግን በሰባተኛው ቀን በክብር ዐርፈዋል። ንጉሡ በሰባት የወርቅ ሣጥኖች ቀብሯቸዋል።

አምላከ አበው ቅዱሳን በመጽናታቸው ያጽናን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ጥር ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ኢትዮጵያዊ (ዕረፍታቸው)
፪.ሰባቱ ደቂቅ ቅዱሳን (ከኤፌሶን)
፫.ቅዱስ አባ ነካሮ
፬.ቅዱስ ቃሮስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ቅዱስ አስከናፍር
፬.አሥራ ሦስት ግኁሳን ጻድቃን
፭.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ
፮.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት

"በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን!"
(፪ቆሮ ፲፫፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ኃያል ቴዎድሮስ በናድሌዎስ <3

በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምሥራቅ (በአንጾኪያ) ያበራ፣
ድንግልናውን በንጹሕ የጠበቀ፣
ቅዱሳን መላእክት የሚያነጋግሩት፣
የአንጾኪያ ሠራዊት ሁሉ አለቃ የነበረ፣
በጦርነት ተሸንፎ የማያውቅ፣
አሕዛብ ስሙን ሲሰሙ የሚንቀጠቀጡለት፣
ከአማልክት ወገን ነው እያሉ የሚፈሩት፣
እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ የሚያመልክ የወቅቱ ወጣት ክርስቲያን ነው።

ዲዮቅልጢያኖስ በካደ ጊዜም ከባልንጀሮቹ ለውንድዮስና ኒቆሮስ ጋር መላእክት ወደ ሰማይ አሳርገውታል። በዚያም መድኃኒታችን ክርስቶስን ፊት ለፊት አይቶ በእሳት ባሕርም ተጠምቋል። በዚህች ቀንም ከቅዱሳን ለውንድዮስና ኒቆሮስ እንዲሁ ከሁለት ሚሊየን አምስት መቶ ሺህ ሰራዊቱ ጋር ለመከራ ተሰጥቷል። እርሱንም በመቶ ሃምሳ ሦስት ችንካር ወግተው ገድለውታል።

አምላከ ቅዱሳን ወይነ ቃና ፍቅሩን ያሳድርብን። ከድንግል እናቱ ምልጃና ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን።

ጥር ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ቃና ዘገሊላ
፪.ቅዱስ ያዕቆብ እስራኤል
፫.ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ
፬.ቅዱሳን ለውንድዮስ እና ኒቆሮስ
፭.ሁለት ሚሊየን አምስት መቶ ሺህ ሰማዕታት (የቅዱስ ቴዎድሮስ ማኅበር)
፮.አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ (ኢትዮጵያዊ)
፯.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፫.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
፭.ቅዱስ ድሜጥሮስ
፮.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ
፯.ቅዱስ አቤሜሌክ ኢትዮጵያዊ
፰.ቅዱስ ባሮክ
፱.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ዘኢየሩሳሌም

"አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ። ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም። ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ 'ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል። ከሰከሩም በኋላ መናኛውን። አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል።' አለው።"
(ዮሐ ፪፥፱-፲)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ።"
መዝ ፻፲፫፥፫
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የጥምቀት በዓል (ኤጲፋንያ) በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 በዓለ ኤጲፋንያ <3

"ኤጲፋንያ" የሚለው ቃል ከግሪክ (ጽርዕ) ልሳን የተወሰደ ሲሆን በቁሙ "አስተርእዮ፣ መገለጥ" ተብሎ ይተረጐማል። በነገረ ድኅነት ምሥጢር ግን ኤጲፋንያ ማለት "የማይታይ መለኮት የታየበት፣ እሳተ መለኮት በተዋሐደው ሥጋ የተገለጠበት" እንደ ማለት ነው።
"ዘኢያስተርኢ ኅቡዕ እስመ አስተርአየ ለነ
እሳት በላዒ አምላክነ።" እንዲል።
(አርኬ)

አንድም ምሥጢር ሆኖ የቆየ አንድነቱ፣ ሦስትነቱ የተገለጠበት ቀን ነውና ዕለተ ጥምቀቱ ኤጲፋንያ ይሰኛል። መድኃኒታችን ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ያድን ዘንድ ከሰማያት ዙፋኑ ወርዶ እንደ ሰውነቱ በሥጋ ማርያም ለሠላሳ ሦስት ዓመታት ተመላልሷል።

ጊዜው ሲደርስም በፈለገ ዮርዳኖስ ከዮሐንስ ዘንድ ሊጠመቅ ሔደ። መድኃኒታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የወረደው ጥር ፲ ቀን አመሻሽ ላይ ሲሆን በፍጹም ትሕትና ተራ ሲጠብቅ አድሮ ሌሊት አሥር ሰዓት ላይ ደረሰውና ሊጠመቅ ቀረበ።

አሥር ሰዓት መሆኑም ርግብ (መንፈስ ቅዱስ) ሲወርድ ሰዎች ሥጋዊት ርግብ ናት ብለው እንዳይጠራጠሩ ነው። ርግብ በሌሊት መንቀሳቀስ አትችልምና።

መድኃኒታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ሲጠጋ አምላክነቱን ተረድቶ "እንዴት ፈጣሪዬ ወደ እኔ ትመጣለህ? እንዴትስ በእኔ እጅ ትጠመቃለህ?" አለው። ትሕትና ለእናትና ልጅ ልማዳቸው ነውና። ጌታ ግን "ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባል።" ሲል እንዲያጠምቀው ፈቀደለት።

ቅዱስ ዮሐንስም "ስመ አብ በአንተ ሕልው ነው። ስመ ወልድ ያንተ ነው። ስመ መንፈስ ቅዱስም በአንተ ዘንድ ሕልው ነው። በማን ስም አጠምቅሃለሁ?" ሲል ጠየቀው።

ጌታ "ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሐለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ" እያልክ አጥምቀኝ አለው። ትርጉሙም "የቡሩክ አብ የባሕርይ ልጁ ብርሃንን የምትገልጥ ሆይ ይቅር በለን! አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዓለም ካህኑ ነህና።" እንደ ማለት ነው።

ከዚያም ጌታ ወደ ዮርዳኖስ ሲገባ ባሕር አይታ ደነገጠች፤ ሸሸችም።
(መዝ. ፸፮፥፲፮ ፤ ፻፲፫፥፫)
ዮርዳኖስ ጨንቆት ግራ ቀኝ ተመላለሰ። እሳተ መለኮት ቆሞበታልና ውኃው ፈላ። በጌታ ትዕዛዝ ግን ጸና።

ጌታ ተጠምቆ፣ ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶ፣ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅጸን አድርጐ፣ የእዳ ደብዳቤአችንንም ቀዶ ከወጣ በኋላ ሰማያት ተከፈቱ። ማለትም አዲስ ምሥጢር ተገለጠ።

አብ በደመና ሆኖ "የምወደው፣ የምወልደው፣ ሕልው ሆኜ ልመለክበት የመረጥኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው!" ሲል በአካላዊ ቃሉ ፍጹም ተዋሕዶን መሰከረ። መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ። ራሱንም ቆንጠጥ አድርጐ ያዘው። በዚህም የሥላሴ አንድነቱ፣ ሦስትነቱ ታወቀ፤ ተገለጠ።

ቅዱስ ዮሐንስ "መጥምቀ መለኮት" የሚባልበትን ታላቁን ክብር ሲያገኝ ዮርዳኖስ የልጅነት መገኛ ቅዱስ ባሕር ሆነ።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

አምላከ ቅዱሳን አበው በፍቅሩ ይገለጥልን። ከአባቶቻችን ጸጋ በረከትም አይለየን።

ጥር ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ አብርሃም ገዳማዊ
፪.አባ ገዐርጊ ጻድቅ
፫.ቅዱስ ዲዮስቅርስ ዘሮሜ
፬.አባ ኪናፎርያ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱሳን ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት
፪.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፫.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
፬.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ
፮.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

"በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው። የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል።
የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው። የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል።"
(ምሳሌ ፲፥፮-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ <3

ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፣ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ።

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)
ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ።

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል።
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ።
(ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው። እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል።

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ። እናንተ በድካማቸው ገባችሁ።" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል።
(ዮሐ. ፬፥፴፮)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፤ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ።" እንዳለ ጌታ በወንጌል።
(ማቴ. ፲፫፥፲፮ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ።

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት፣ አራቱ ዐበይት ነቢያት፣ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ።

አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት፦
ቅዱስ አዳም አባታችን
ሴት
ሔኖስ
ቃይናን
መላልኤል
ያሬድ
ኄኖክ
ማቱሳላ
ላሜሕ
ኖኅ
አብርሃም
ይስሐቅ
ያዕቆብ
ሙሴና
ሳሙኤል ናቸው።

አራቱ ዐበይት ነቢያት፦
ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
ቅዱስ ኤርምያስ
ቅዱስ ሕዝቅኤልና
ቅዱስ ዳንኤል ናቸው።

አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት፦
ቅዱስ ሆሴዕ
አሞጽ
ሚክያስ
ዮናስ
ናሆም
አብድዩ
ሶፎንያስ
ሐጌ
ኢዩኤል
ዕንባቆም
ዘካርያስና
ሚልክያስ ናቸው።

ካልአን ነቢያት ደግሞ፦
እነ ኢያሱ
ሶምሶን
ዮፍታሔ
ጌዴዎን
ዳዊት
ሰሎሞን
ኤልያስና
ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው።

ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ።
የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እስራኤል)ና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ።

በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦
ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)፣
ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)፣
ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ።
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ።

ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፰፻ ዓ/ዓ አካባቢ ነው። "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው። አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል።

ሚክያስ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል። ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው። አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው። የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው።

ቅዱሱ ነቢይ ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር። በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም። ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር። በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ። በሦስቱ ነገሥታት (በኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል። ሕዝቡን፣ መሳፍንቱን፣ ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል።

አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ። ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት።
"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ - አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም። ወገኖቼን እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ካንቺ ዘንድ ይወጣልና።" አለ።

ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በኋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል። በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል።

ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ ሰባት ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ በመልካም ሽምግልና በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል። ወገኖቹም ቀብረውታል። ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል።

አምላከ ቅዱሳን ለተፋቅሮ ይበለን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ጥር ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ
፪.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ
፫.አባ እንድራኒቆስ ሊቀ ጳጳሳት
፬.አባ ብንያሚን ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፫.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፬.አቡነ ኪሮስ
፭.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

"ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን?
.....ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል። እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ ምሕረትንም ትወድ ዘንድ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?"
(ሚክ ፮፥፮-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ <3

የሊብያው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ስምንት ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ።

ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና ምግባራቸው የጸና ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ።

እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን። ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው።

እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው። እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና መገለጫ እንመልከት።
፩.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (በዘመነ ሰማዕታት ለሃያ ሁለት ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ፣ እግር፣ ጆሮ፣ ከንፈር፣ ቅንድብ ነው።)
፪.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ (ስለ ቀናች እምነት ለሃምሳ ዓመታት የተጋደለና ለአሥራ አምስት ዓመታት በስደት የኖረ አባት ነው።)
፫.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው።)
፬.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ (በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ፣ ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው።)
፭.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ (ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጓድ ውስጥ ለአሥራ አምስት ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው።)
፮.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ (ከሕፃንነቱ የተቀደሰ፣ በበርሃ የተጋደለ፣ በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው።)
፯.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ፣ ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ፣ በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው።)
፰.ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ (ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ፣ ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው።)
፱.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ (ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው።)

እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት!) ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው።

ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ (ኢሳ. ፱፥፮ ፣ መዝ. ፵፮፥፭ ፤ ፸፯፥፷፭ ፣ ዘካ. ፲፬፥፬ ፣ ዮሐ. ፩፥፩ ፤ ፲፥፴ ፣ ራእ. ፩፥፰ ፤ ሮሜ. ፱፥፭.....) አርዮስና የዛሬ መሰሎቹ አንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል።

በወቅቱም በመወገዙ አርዮስ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ። ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውንት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ።

በ፫፻፳፭ ዓ/ም (በእኛው በ፫፻፲፰ ዓ/ም) ለአርባ ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ። ሱባኤውን ሲጨርሱም በአራቱ ፓትርያርኮች (እለእስክንድሮስ፣ ሶል ጴጥሮስ፣ ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ) መሪነት፣ በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት፣ በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ።

በጉባኤው ሙሉ ሥልጣን በሰማይ ከፈጣሪ በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት። ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ፣ ሥግው ቃል፣ ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት።

በጉባኤው መጨረሻም አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ። አባቶችም ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል።

ቅዱስ ሶል ጴጥሮስም ከጉባዔው ከተመለሰ በኋላ በጐ ጐዳናውን አቅንቶ ቀጥሏል። ብዙ ድርሳናትን ደርሶ በድካም ሰብኮ ኢአማንያንን መልሷል። ፈላስፎችንም ድል ነስቶ አሳምኗል። መናፍቃን ደግሞ ፈጽመው ይፈሩት ነበር። ሊቀ ጵጵስናን በተሾመ በአሥራ አንድ ዓመቱም በዚህች ቀን ዐርፏል።

የሥላሴ ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን።

ጥር ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.በዓለ ሥሉስ ቅዱስ
፪.ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ
፫.ቅዱስ ኤፍሬም
፬.ቅዱስ ሰሎሞን

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፪.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፫.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፬.አባ ባውላ ገዳማዊ
፭.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፮.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

"የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።"
(፪ቆሮ ፲፫፥፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥር ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.በዓለ ግዝረቱ ለክርስቶስ
፪.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፫.ቅዱስ ኖኅ ጻድቅ
፬.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፭.አባ ሙሴ ገዳማዊ
፮.አባ ወርክያኖስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፬.ቅድስት ሰሎሜ
፭.አባ አርከ ሥሉስ
፮.አባ ጽጌ ድንግል
፯.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ በማኅጸን ሳይገረዝ በመልአኩ እንደ ተባለ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ።"
(ሉቃ ፪፥፳፩)

"እውነት እውነት እላችኋለሁ። በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል። ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል።"
(ዮሐ ፲፬፥፲፪)

"ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝኩትን የባሪያዬን የሙሴን ሕግ አስቡ። እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።"
(ሚል ፬፥፬-፮)

"እግዚአብሔርም፦ 'የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ። ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና።' አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።
የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበር። ኖኅ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።"
(ዘፍ ፮፥፯-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…
Subscribe to a channel