gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ አባ አውሎግ እና ቅዱስ በላትያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ አውሎግ አንበሳዊ <3

አባ አውሎግ ማለት፦
ከቀደመው ዘመን ጻድቃን አንዱ፣
እንደ ገዳማውያን ፍፁም ባሕታዊ፣
እንደ ሐዋርያት ብዙ ሃገራትን በስብከተ ወንጌል ያሳመኑ፣
በግብጽና በሶርያ በርሃዎች ለዘጠና ዓመታት የተጋደሉ ጻድቅና ሐዋርያ ሲሆኑ የሚጓዙበትና የሚታዘዛቸው ግሩም አንበሳ ነበር።
በዚህም አባ አውሎግ "አንበሳዊ" ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጠራቸዋለች።

አባ አውሎግ ከሚታወቁበት አገልግሎት አንዱ ስብከተ ወንጌል ነው። ምንም እንኳ ገዳማዊ ቅዱስ ቢሆኑም ያላመኑትን ለማሳመን ያመኑትንም ለማጽናት ተጋድለዋል።

እግዚአብሔር በሰጣቸው አናብስት በአንዱ ላይ ተጭነው (መዝ. ፺፥፲፫) በሌላኛው ላይ እቃቸውን አስቀምጠው በየአኅጉራቱ ከመምህራቸው ቅዱስ አውሎጊን ጋር ይዘዋወሩም ነበር። የጌታ ቸርነት ሆኖም አናብስቱ የቅዱሳኑን ፈቃድ ሳይነገራቸው ያውቁ ነበር።

ሲርባቸውም ተግተው ይመግቧቸው ነበር። እንዲያውም አንዴ ቅዱሳኑ እንደራባቸው አንዱ አንበሳ ሲያውቅ ከበርሃ ወደ ገበያ መንገድ ወጥቶ ተመለከተ። በአህያ ላይ ልጁንና ስንቁን (ዳቦ) ጭኖ የሚሔድ ሽማግሌ ነበርና ዳቦውን አንስቶ ወስዶ ለእነ አባ አውሎግ ሰጣቸው።

ከድንጋጤ የተነሳም ሕፃኑ ሙቶ ነበርና ሽማግሌ አባቱ አዘነ። አንበሳው ግን ሕፃኑንም ወደ ቅዱሳኑ ወስዶ አስረከበ። ቅዱሳኑም ከሕብስቱ በመጠናቸው በልተው ቢባርኩት እንዳልተበላ ሆነ። ሕፃኑንም ከሞት በጸሎታቸው አስነስተው ለአንበሳው ሰጥተውታል።

አንበሳውም ስንቁንና ልጁን ለአረጋዊው ሰጥቶት በደስታ ወደ ሃገሩ ተመልሷል። ቅዱስ አባ አውሎግና መምህሩ አውሎጊን ከዘጠና ዓመታት በላይ በዘለቀ ተጋድሏቸው አጋንንትን ያሳፍሩ ዘንድ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሕ መስዋዕት ይሆኑለት ዘንድ በትጋት ኑረዋል።
ብዙ ተአምራትን ሠርተው ፈጣሪያቸውን አክብረዋል።
እንደ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ባሕር ከፍለዋል።
እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙት አንስተዋል፤ ድውያንን ፈውሰዋል።
እንደ ቅዱስ ዳንኤል አናብስትን ገዝተዋል።
ይህች ቀን ዕለተ ዕረፍታቸው ናት።

<3 ቅዱስ በላትያኖስ <3

ይህ ቅዱስ ሐዋርያዊ ጳጳስ የቀድሞዋ ሮም ሊቀ ጳጳሳት ሲሆን ቸር፣ ትጉህና በጐ እረኛ ነበር። መናፍቃንን ሲያርም፣ ምዕመናንን ሲመክር፣ ስለ መንጋው እንቅልፍ አጥቶ ኑሯል። በፍጻሜውም በዚህች ቀን የሮም ንጉሥ ለአንድ ዓመት አሰቃይቶ ገድሎታል። ዕሴተ ኖሎትን (የእረኝነት ዋጋንም) ከጌታችን ተቀብሏል።

አምላከ አበው ቅዱሳን በመጽናታቸው ያጽናን። ከበረከታቸውም ያድለን።

የካቲት ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ አውሎግ አንበሳዊ
፪.አባ አውሎጊን ጻድቅ (የአባ አውሎግ መምህር)
፫.አባ በላትያኖስ ሰማዕት (የሮም ሊቀ ጳጳሳት)
፬.አባ በትራ (የጻድቁ አባ ስልዋኖስ ደቀ መዝሙር)
፭.አባ አብርሃም ኤጲስ ቆጶስ
፮.አባ መቃቢስ
፯.አባ ኮንቲ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፬.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
፭.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

"በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምንም ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ ነው።"
(ኤፌ ፩፥፲፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባታችን ታላቁ ቅዱስ በርሱማ ሶርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ አባ በርሱማ <3

ታላቁ (THE GREAT ይሉታል።) አባ በርሱማ በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ምንኩስናና ገዳማዊ ሕይወትን ያስፋፋ አባት ነው።

በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምድረ ሶርያን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች የቅድስና ሕይወትን ያስፋፋው ቅዱስ በርሱማ ለቤተ ክርስቲያን ምሰሶ ከሆኑላት አበው አንዱ ነው። እርሱ ከተጋድሎው ብዛት ለሃምሳ አራት ዓመታት ያለ እንቅልፍ ቆይቷል።

በእነዚህ ዘመናትም ግድግዳ ላይ ጠጋ ብሎ ከማረፉ በቀር መቀመጥን እንኳ አልመረጠም። በመዓልትም በሌሊትም በፍቅር አብዝቶ ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ በመጸለዩ የብዙዎቹን ነፍስ ወደ ሕይወት ማርኳል።

ገዳማትን ከማስፋፋትና ደቀ መዛሙርትን ከማብዛቱ ባለፈ በስብከተ ወንጌልም የተመሰከረለት አባት ነበር። በ፬፻፴፩ (፬፻፳፫) ዓ.ም በኤፌሶን በተደረገው የቅዱሳን ጉባኤ ላይ ከተገኙ ሊቃውንትም አንዱ ነው። በቅድስና ሕይወቱ የተገረመው የቁስጥንጥንያው ንጉሥ (ትንሹ ቴዎዶስዮስ) የንግሥና ቀለበቱን እና ማኅተሙን ሸልሞታል።

ቅዱሱም የዋዛ አልነበረምና በንጉሡ ማኅተም እያተመ "ተፋቀሩ" የሚሉ ብዙ አዋጆችን ወደ መላው ዓለም ልኳል። በ፬፻፶፩ (፬፻፵፫) ዓ.ም በኬልቄዶን ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ሰነፍ ጳጳሳት ጉባኤ አድርገው አባ ዲዮስቆሮስን እንደ ገደሉት ሲሰማም ወደ ቤተ መንግሥት ሒዶ ከሃዲዎቹን (መርቅያንና ሚስቱ ብርክልያን) በአደባባይ ዘልፏቸዋል።

ስለ አዘነባቸውም ተቀስፈዋል። ታላቁ ቅዱስ አባ በርሱማ ፀሐይን ማቆሙን ጨምሮ በርካታ ተአምራትን ሠርቶ በዚህች ቀን ዐርፏል።

ቸር አምላኩ ከበረከቱ ይክፈለን።

የካቲት ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ) የመነኮሱበት በዓል
፫.ቅዱስ ጳውሎስ ሶርያዊ (ሰማዕት)
፬.ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
፪.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፫.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
፬.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

"ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን?.....
ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል። እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ ምሕረትንም ትወድ ዘንድ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?"
(ሚክ ፮፥፮-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ አባታችን አባ አብዱልማዎስ ገዳማዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ አብዱልማዎስ ገዳማዊ <3

ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆኑ በበርሃ ሰው ሳያዩ ለሰባ ዓመታት በቅድስና ኑረዋል። በጊዜውም እግዚአብሔር አባ አብዱልማዎስን ወደ አባ ዕብሎይ ልኳቸው ነበር። ሁለቱ ተገናኝተው አብረው ለሦስት ቀናት ሲቆዩ ቅዱስ መልአክ እየተገለጸ አጽናንቷቸዋል። ከሥውራን ማኅበርም ተቀላቅለው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለዋል።

አባ ዕብሎይ ሲያርፍ አንበሶች እያገዟቸው ቀብረዋቸዋል። እርሳቸውም "እኔን የሚቀብረኝ ስጠኝ።" ብለው ጸልየው ነበርና ሦስት ገዳማውያን መጥተውላቸዋል። የካቲት ፭ ቀን አባ ዕብሎይን ገንዘው ቀብረው በሦስተኛው ቀን አርፈዋል።

የአብ በረከት፣ የወልድ ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት፣ የድንግል ማርያም ምልጃ፣ የቅዱሳኑ ጸጋ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን።
የጻድቁ ክብር ይደርብን።

የካቲት ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ አብዱልማዎስ ገዳማዊ
፪.አባ ቴዎድሮስ ሊቀ ጳጳሳት
፫.አባ እለ እስክንድሮስ ሊቀ ጳጳሳት
፬.ቅዱስ አባዲር

ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ

"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ። ሐሴትም አድርጉ።"
(ማቴ ፭፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባ ብሶይ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዕብሎይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ብሶይ (ጴጥሮስ) <3

ብሶይ (ቢሾይ) በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተለመደ የቅዱሳን ስም ነው። በተለይ በምድረ ግብጽ በዚህ ስም ሰማዕታትም ጻድቃንም ተጠርተውበታል። ከእነዚህ ቅዱሳን (ከገዳማውያኑ) አንዱ የሆነው አባ ብሶይም (አንዳንዴ አባ ጴጥሮስም ይባላል።) የዘመነ ጻድቃን ፍሬ ነው።

ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ቤት ናት። ያ ማለት ራሳቸውን ለክርስቶስ የለዩ ሰዎች ይኖሩባታል። እነዚህ ሰዎች ከተለያየ ጐዳና እና ማንነት ሊመጡ ይችላሉ። ቢያንስ ግን በንስሐ የታጠቡ መሆናቸው ወደ ተቀደሰው አንድነት እንዲገቡ ትልቅ መሠረት ይሆናቸዋል።

ቅዱሳንም አንዳንዶቹ ከእናታቸው ማኅጸን ሲመረጡ ሌሎቹ ደግሞ ከኃጢአት ሕይወት የተመለሱ ሆነው ይታያሉ። ደስ የሚለው ደግሞ በንስሐ ከታጠቡ በኋላ በፍጹም ልባቸው በመጋደላቸው እነሆ በሰማያዊ አክሊል ተከልለዋል።

አባ ብሶይ ጴጥሮስም ከኃጢአት ተመልሰው ለቅድስና ከበቁ ቀደምት አበው አንዱ ነው። ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ምድረ ግብጽ የታወቀ ሽፍታ፣ ዝሙተኛና ክፋቱ የተገለጠ ሰው ነበር። ለብዙ ዘመናት በእንዲህ ካለ ግብሩ መላቀቅ ባይችል እግዚአብሔር ጥሪውን ላከለት።

የአምላካችን የጥሪ መንገዱ ብዙ ነውና ለእርሱ ደዌን ላከለት። መቼም ወደድንም ጠላንም በሽታ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ጥሩ ፈሊጥ (አጋጣሚ) ነው። ዛሬም ቢሆን ዘለን ዘለን ስንሰበርና የሐኪም መፍትሔ ሲጠፋ የግዳችን ወደ እግዚአብሔር ቤት (ወደ ጠበሉ) እንቀርባለንና። አምላካችን ስለዚህ ጥበቡ ይክበር ይመስገን።

ቅዱስ አባት ብሶይም በሽፍትነትና በኃጢአት ኑሮ ሳለ ለሞት የሚያበቃ ደዌ ደርሶበት የአልጋ ቁራኛ ሆነ፤ ኃይሉም ደከመ። በእንዲህ እያለም በራእዩ ያየው ነገር ፍጹም አስደነገጠው። መላእክት ነፍሱን ወስደው መካነ ኩነኔን ካሳዩት በኋላ አለቀሰ።

ይልቁን ሌቦችና ዝሙተኞችን ከአራት ሲቆራርጣቸው ስላየ ፈጽሞ አዘነ፤ ተጸጸተ። ፈጣሪውንም ዕድሜ ለንስሐ እንዲሰጠው ተማጸነ። ጌታንም "አምላኬ ሆይ! ከበሽታዬ ብታድነኝ ዳግመኛ አልበድልህም። ዓለምን ሁሉም ንቄ አገለግልሃለሁ።" ሲል ተማጸነው።

እግዚአብሔርም ሰምቶት ፈጥኖ ፈወሰው። አባ ብሶይም እንደ ቃሉ በፍጹም ልቡ ንስሐ ገብቶ መነነ። በገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ሲኖር የላመ የጣመ በልቶ ከሞቀ መኝታ ተኝቶ አያውቅም።

ሰውነቱን ይቀጣት ዘንድም እስከ ሠላሳ ቀን ያለ እህል ውኃ ይጾም ነበር። በዘመኑ ሁሉም የሴት መልክን አላየም። ንስሐን የሚወድ ጌታም ጸጋውን አብዝቶለት ብዙ ድርሳናትን ጽፏል። የሚገርመው ደግሞ ከትህትናውና ቅድስናው የተነሳ የእያንዳንዱ ሰው ኃጢአት ተገልጦ ይታየው ነበር።

ቅዱሱ አባታችን ብሶይ ጴጥሮስ በንስሐና በቅድስና ሕይወት እንዲህ ተመላልሶ በዚህች ቀን ዐርፎ በገዳሙ ተቀብሯል። የድካሙን ዋጋም አድልዎ ከሌለበት ከእውነተኛው ፈራጅ ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብሏል።

<3 ቅዱስ ዕብሎይ <3

አባ ዕብሎይ በቀደመ ሕይወቱ ለአርባ ዓመታት በኃጢአት የኖረ፣ እግዚአብሔር ለንስሐ ሲጠራው "እሺ" ብሎ ለአርባ ዓመታት በንስሐ ሕይወት ተመላልሶ በበርሃ የተጋደለ፣ እንባው እንደጐርፍ ይፈስ የነበረ፣ አጋንንትንም ድል የነሳና ለፍሬ ለትሩፋት የበቃ ቅዱስ አባት ነው። እግዚአብሔርም ብዙ ቃል ኪዳን ገብቶለታል።

"ባርያ ሆኖ ያለ ኃጢአት ጌታ ሆኖ ያለ ምሕረት የለምና ይቅር በለን!"
(የአባ ዕብሎይ የንስሐ ጸሎት)

አምላከ ቅዱሳን ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ አይንሳን። ከክብረ ቅዱሳንም ያካፍለን።
አምላክ በበረከታቸው ይባርከን።

የካቲት ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ብሶይ ጻድቅ
፪.ቅዱስ አባ ዕብሎይ ገዳማዊ
፫.አባ አክርጵዮስ
፬.አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት (ፍልሠታቸው)
፭.ቅዱስ አሞኒና ሚስቱ ቅድስት ሙስያ (የታላቁ ዕብሎይ ወላጆች)
፮.አባ ኖብ ጻድቅ መነሳንሱ ዘወርቅ
፯.ቅዱሳን አባ አሞኒና አባ ዮሐኒ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
፫.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፭.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ

"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል። ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ።' ይላቸዋል። እላችኋለሁ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።"
(ሉቃ ፲፭፥፬-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለማሪ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እና ለአበው አባ ያዕቆብ ወአባ ዕብሎይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ <3

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ፪፻፺፰ (፫፻፮) ዓ.ም ነው። ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ። (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም።)

ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር። የሰማዕትነት፣ የሐዋርያነት፣ የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው። ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ።

ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምህርት ነው። የሚገርመው መምህሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይህንኑ አጥብቆ አስተምሮታል።

ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር። ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና። እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት ይገዛላትም ገባ።

በጊዜው እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር። እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን (ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት፣ ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር።

በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ፫፻፲፰ (፫፻፳፭) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምህረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምህርትና በረከትን አግኝቷል።

ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራእይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይህማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው።" አለው። እርሱም መምህሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ። ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል።

በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል። ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር። ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር። "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ እንደ እንጀራ ተመግቤው እንደ ውኃ ጠጥቼው እንደ ልብስም ተጐናጽፌው።" እያለ ይመኝ ነበር።

አፍጣኒተ ረድኤት ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት። ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት። ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ በፊቱ ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ በፊቷ ቆሞ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ነው።

ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች። ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል። ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው።

እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ - የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ።" ብሎ ጸልዩዋል። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ "ተክሪት" በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል።

በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል። የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል። ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል። በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል፤ ተአምራትንም ሠርቷል። በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ፫፻፷፭ (፫፻፸፫) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል።

ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል።
ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን፦
፩.ቅዱስ ኤፍሬም
፪.ማሪ ኤፍሬም
፫.አፈ በረከት ኤፍሬም
፬.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም
፭.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም
፮.አበ ምዕመናን ኤፍሬም
፯.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም አባታችን አንተ ነህ!
ዛሬ ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዓመታዊ የፍልሠት በዓሉ ነው።

ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን፣ ክብሩን፣ አእምሮውን፣ ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን፤ አሳድሪብን። አሜን!

<3 አባ ያዕቆብ ገዳማዊ <3

ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት "ለስሒት መኑ ይሌብዋ - ስሕተትን ማን ያስተውላታል።" (መዝ. ፲፰፥፲፪) ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ታላቅ ቅዱስ ሰው በኃጢአት ብዙ ተፈተነ። ወደ በርሃ ወጥቶ በምናኔ ጸንቶ በጾምና በጸሎት ተግቶ ዘመናትን ስላሳለፈ ሰይጣንን አሳፈረው።

ግን ደግሞ ክፉ ጠላት ባልጠረጠረው መንገድ መጥቶ መከራ ውስጥ ከተተው። የአገረ ገዢው ልጅ ታማ "ፈውሳት" አሉት፤ እርሱም ፈወሳት። ወደ ቤቷ ስትመለስ ግን አመማት። "ከአንተ ጋር ትቆይ።" ብለው ትተዋት ቢሔዱ ከመለማመድ የተነሳ በዝሙት ወደቀ።

እንዳይገለጥበት ስለ ፈራም ገደላት። በሆነው ነገር ተስፋ ቆርጦ ወደ ዓለም ሲመለስ ቸር ፈጣሪ የሚናዝዝ አባትን ልኮ ንስሐ ሰጠው። ጉድጓድ ምሶ ድንጋይ ተንተርሶ ለሠላሳ ዓመታት አለቀሰ። እግዚአብሔርም ምሮት የቀደመ ጸጋውን ቢመልስለት ዝናምን አዝንሞ ሕዝቡን ከእልቂት ታድጓል። በዚህች ዕለት ዐርፎም ለርስቱ በቅቷል።

<3 ታላቁ አባ ዕብሎይ <3

ይህ ቅዱስ የአቡነ አቢብ ደቀ መዝሙር ሲሆን በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳንም ቀዳሚው ነው። ብዙ መጻሕፍት "ርዕሰ ገዳማውያን" ይሉታል። የቅዱሱ ተጋድሎ እጅግ ሰፊ ነው።

የአባቶቻችን በረከት ይደርብን።

የካቲት ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፪.አባ ያዕቆብ መስተጋድል
፫.ቅዱስ አባ ዕብሎይ ገዳማዊ (ሕይወቱ መላእክትን የመሰለ ግብጻዊ አባት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም
፪.ቅዱስ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት
፫.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፬.ቅዱሳን ዘካርያስ ወስምዖን
፭.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፮.አባ ዜና ማርቆስ ጻድቅ
፯.አባ መድኃኒነ እግዚእ (ዘደብረ በንኮል)

"ለምኑ ይሰጣችሁማል። ፈልጉ ታገኙማላችሁ። መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና። የሚፈልገውም ያገኛል። መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል።"
(ማቴ ፯፥፯-፰)

"የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፴-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ገዳማዊ አባ ጳውሊ እና ለጻድቁ አባ ለንጊኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ ቅዱስ ጳውሊ <3

በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ /ዐቢይ/ THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው። አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን።

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው። በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል። ሕይወቱ በጐላ በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው።

ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል።

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለአርባ ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል፤ አስተምሯል። በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት።

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። አኗኗራቸውም በቡድንም በነጠላም ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው። ይህም ሲያያዝ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደረሰ። በዚህ ዘመን ግን አባ ጳውሊ የሚባል ንጹሕ ክርስቲያን ይህንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው። ለሰማንያ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ። ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ።

ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት። በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ። ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ።

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል። ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል።

አንድ ቀን ቅዱስ እንጦንስ (የመነኮሳት ሁሉ አባት) እንዲህ ሲል አሰበ። "በውኑ በበርሃ ለበርካታ ዘመናት በመኖር ከእኔ የሚቀድም (የሚበልጥ) ሰው ይኖር ይሆን?"
ይህንን ሃሳቡን ገና ሳይጨርሰው ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ ዘንድ ደረሰ።

"እንጦንስ ሆይ! ከእኔ የሚቀድም የበርሃ ሰው ይኖር ይሆን ብለህ አስበሃል። በእርግጥም ከአንተ ሃያ ዓመታትን ቀድሞ ወደ በርሃ የገባ፣ በቅድስናው ፈጣሪውን ያስደሰተ፣ ዓለም ከነ ክብሯ የእግሩን መረገጫ ያህል እንኳ የማትመጥነው በጸሎቱና በምልጇው ዓለም የምትጠበቅለት ሞገስን የተሞላ አንድ ሰው በበርሃ ስላለ ሒድና ተመልከተው።" ብሎት ተሠወረው።

ቅዱስ እንጦንስም ከሰማው ነገር የተነሳ እየተደነቀ ተነሳ። እርሱ ካለበት በርሃ በራቀ መንገድም ለቀናት ተጉዞ አንድ በዓት (ዋሻ) በር ላይ ደረሰ። በበሩ አካባቢ የሰውና የአራዊት ኮቴ ተመልክቶ በሩን ጸፋ (ቆፈቆፈ)። በውስጥ ያለው አረጋዊ ሰው ግን ትልቅ ድንጋይ ገልብጦ በሩን አጠበቀው። ለሰማንያ ዓመታት ሰውን አይቶ አያውቅምና ሰይጣን ሊያታልለኝ መጥቷል ብሎ አስቧል። ቅዱስ እንጦንስ ግን "ኃሠሥኩ እርከብ ጐድጐድኩ ይትረኃው ሊተ - ሽቻለሁና ላግኝ፤ ደጅ መትቻለሁና ይከፈትልኝ።" ሲል አሰምቶ ተናገረ።

ቅዱሱ ገዳማዊም ሰው መሆኑን ሲያውቅ በሩን ከፈተለትና ወደ ዋሻው አስገባው። መንፈሳዊ ሰላምታንም ተለዋወጡ። ሲመሽም ቅዱስ እንጦንስ ሽማግሌውን ገዳማዊ "ስምህ ማን ነው?" ቢለው "ስሜን ካላወክ ለምን መጣህ?" ሲል መለሰለት።

ያን ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ቀና ብሎ ሰማይን ሲመለከት ምሥጢር ተገለጠለትና "ቅዱስ ጳውሊ ሆይ! ከአንተ ጋር ያገናኘኝ ፈጣሪ ይክበር፤ ይመስገን።" ሲል ፈጣሪውን ባረከ። ቅዱስ ጳውሊም መልሶ (በጸጋ አውቆት) "አባ እንጦንስ ሆይ! እንኳን ደህና መጣህ።" አለው። ሁለቱም ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ተጨዋወቱ።

ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ዓይነት የቅድስና ሕይወት የመጀመሪያ የምትላቸው አላት። ለምሳሌ፦
የመጀመሪያው ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስ፣
የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ፣
የመጀመሪያው ባሕታዊ (ገዳማዊ) ቅዱስ ጳውሊ እና የመጀመሪያው መነኮስ ቅዱስ እንጦንስን ማንሳት እንችላለን።

ቅዱስ ጳውሊ የተወለደው በሰሜናዊ ግብጽ በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው። ወላጆቹ ባለጸጐች ነበሩ። ቅዱሱንና ታላቅ ወንድሙን አባ ጴጥሮስን ወልደዋል። ሁለቱ ክርስቲያን ወንድማማቾች ገና ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው። ሃዘናቸውን ፈጽመው ሃብት ሲካፈሉ ግን መስማማት አልቻሉም።

ምክንያቱ ደግሞ ትልቁ ጴጥሮስ ደህና ደህናውን እቃ ወስዶ መናኛ መናኛውን ለትንሹ ለጳውሎስ (ጳውሊ) መስጠቱ ነበር። ስለዚህ ነገር ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሔዱ ግን መንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሙቶ ደረሱ።

ቆመው ሳሉም ቅዱስ መልአክ ሰው መስሎ ጳውሊን "ይህ ሰው ባለጸጋ ነው። በገንዘቡ የሰጠውን ፈጣሪ ሲበድልበት ኑሮ እነሆ ተሸኘ። በሰማይም አስጨናቂ ፍርድ ይጠብቀዋል።" ሲል ነገረው።

በዚያች ቅጽበት የወጣቱ ጳውሊ ሐሳብ ተለወጠ። ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ! ሁሉ ንብረት ያንተ ይሁን።" ብሎት ከአካባቢው ጠፋ። በመቃብር ሥፍራ ለሦስት ቀናት ያለ ምግብ ጸልዮ የእግዚአብሔር መልአክ ሰው ወደ ማይደርስበት በርሃ ወሰደው።

በዚያም ምንጭ ፈለቀችለት። እየጾመ ይጸልይ ይሰግድ ገባ። ሁሌ ማታ ግማሽ ሕብስት ከሰማይ እየወረደለት ቅዳሜና እሑድ መላእክት እያቆረቡት ለሰማንያ ዓመታት ኖረ። (አንዳንድ ምንጮች ግን ለዘጠና ዓመታት ይላሉ።) ከቅዱስ እንጦንስ ጋር የተገናኙትም ከዚህ በኋላ ነው።

ከቅዱስ እንጦንስ ጋር በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታም ቅዱስ ጳውሊ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል። በዚህች ቀን ሲያርፍም መቃብሩን አናብስቱ ቆፍረዋል። ቅዱስ እንጦንስም በክብር ቀብሮታል። ለሰማንያ ዓመታት የለበሳት የዘንባባ ልብሱም ሙት አስነስታለች።

ጻድቅ፣ ቡሩክ፣ ቀዳሚው ገዳማዊ፣ መላእክትን የመሰለና የባሕታውያን ሁሉ አባት ለተባለ ለቅዱስ ጳውሊ ክብር ይገባል!

<3 አባ ለንጊኖስ <3

ጻድቁ ከኪልቅያ እስከ ሶርያ ከሶርያ እስከ ግብጽ ድረስ በተጋድሎ የተጓዙ አባት ናቸው። በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽም የደብረ ዝጋግ (ግብጽ፤ እስክንድርያ) አበ ምኔት ሆነው አገልግለዋል።

ሙታንን አስነስተው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። ከድንቅ ነገራቸው ሰይጣን የእርሳቸውን የምንኩስና ቆብ ዐይቶ ደንግጦ መሸሹን እንጠቅሳለን።
"ኀበ ኢኀሎከ ሶበ ቆብዓከ ርዕየ
ሰይጣን ተኃፊሮ እፎኑመ ጐየ።" እንዲል።
(አርኬ)

አምላክ በበረከታቸው ይባርከን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ እንዲሁም ይጨምርብኝ።"
ሩት ፩፥፲፯

ቤተ ክርስቲያን እናታችን ናት። የወለደችን እናታችን፤ ከማርና ከወተት ይልቅ የሚጣፍጥ ቃሉን መግባ ያሳደገችን። ቤቷ አንድም ቀን ጎድሎባት የማያውቅ ለወደፊትም የማይጎድልባት ስንዱ እመቤት። በደስታ ቤቷ ሔደን "እግዚአብሔር ይመስገን።" ብለን ደስታችንን የምናካፍላት ሲከፋንና ሲጨንቀን እናቴ ሆይ ብለን ጭንቀታችንን የምንነግራት፤ በሐዘናችን የምታዝን በደስታችን የምትደሰት እናት።

ምንም እንኳን ከጠፉ በጎች መካከል ብሆንም ዘወትር በንስሐ እመለስ ዘንድ ሳትታክት ድምጿን ከፍ አድርጋ የምትጠራኝ፤ ዘወትር ስለ እኔ "እግዚአብሔር እንዳይቀየማቸው ከመዓትም ተመልሶ ፍጹም ዕረፍትን ይሰጣቸው ዘንድ ስለበደሉ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን እንማልዳለን።" ብላ በጸሎቷ የምትማልድልኝ የፍቅር እናት።

ከዚህ ምድር በሞት ስለይ እንኳ የመጨረሻ ቤቴ አንቺ ነሽ፤ በየዕለቱ "ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወገን ስለሞቱ ሰዎች እግዚአብሔር የዕረፍት ቦታ ይሰጣቸው ዘንድ እንማልዳለን።" ብለሽ የምታስቢኝ የዕረፍት ቦታን አገኝ ዘንድ የምትለምኝልኝ ጽኑ እናቴ።

እኔን ከአንቺ የሚለየኝ የለም!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ለሃይማኖቴ አንገቴን እሰጣለሁ!

እንኳን ለጾመ ነነዌ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጾመ ነነዌ ወቅዱስ ዮናስ ነቢይ <3

ዮናስ ማለት 'ርግብ፤ የዋህ' ማለት ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው። በሰራፕታ ተወልዶ ያደገው ነቢዩ በልጅነቱ ታሞ ሙቶ ነበር። ታላቁ ነቢይ ኤልያስ ግን ሰባት ጊዜ ጸሎት አድርጐ ከሞት አስነስቶታል። (፩ነገ. ፲፯፥፲፯) እናቱ የሰራፕታዋ መበለትም ደግ ሴት ነበረች።

ቅዱስ ዮናስ በእድሜው ከፍ ሲል የቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙር ሆነ። የነ ኤልሳዕና አብድዩም ባልንጀራ ነበረ። ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ካረገ በኋላ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንት መቶ ዓመት አካባቢ የነነዌ ሰዎች ኃጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ።

"ሒድና ለነነዌ ሰዎች ንስሐን ስበክላቸው" አለው።። ከነቢያት ወገን ከሙሴና ከዳዊት ቀጥሎ የዮናስን ያህል የዋህ (ገራገር) የለምና እንቢ አለ። (ሰምቶ ዝም አለ።) እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል!" ብሎ ወደ ተርሴስ ኮበለለ።

ወገኖቼ አንድ ነገርን ልብ እንበል። እንኳን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮናስ እኛ ክፉዎችም ከጌታ ፊት መሸሽ እንደማይቻል ጠንቅቀን እናውቃለን።
ታዲያ ለምን ሸሸ ቢሉ፦
ጥበበ እግዚአብሔር በውስጡ ስለ ነበረበት ነው። ምክንያቱም ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ኖሮ ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ ለጌታ ትንሣኤ ጥላ (ምሳሌ) ነው። ለዚህም ምስክሩ ራሱ ጌታችን ነው።
"ወበከመ ነበረ ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ ዕለተ ወሠሉሰ ለያልየ ከማሁ ይነብር ወልደ እጓለ እመ ሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ ዕለተ
ወሠሉሰ ለያልየ" እንዲል።
(ማቴ. ፲፪፥፴፱)

ቅዱስ ዮናስ በገንዘቡ ዋጅቶ ወደ መርከብ በገባ ጊዜ ታላቅ ማዕበል ሆነ። የእምነት ሰው ነውና እንዲያ እየተናወጡ እርሱ በእርጋታ ተኝቷል። እነርሱ ግን ቀስቅሰው ቢጠይቁት (እጣ ወድቆበታልና።) "የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ።" አላቸው።

እያዘኑ ቢጥሉት ታላቅ ጸጥታ ሆነ። እነዚያ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመስዋዕትና በስዕለት አከበሩ። ዮናስ ግን በማዕበልና በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት ጸለየ። ዓሣ አንበሪው በሦስተኛው ቀን ወደ ነነዌ ተፋው።

ቅዱሱም "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዐባይ ሃገር።" እያለ ንስሐን ሰበከ። የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን አምነው ቢጸጸቱ ከሰማይ ወርዶ ከደመና ደርሶ የነበረው የእሳት ማዕበል ተመልሶላቸዋል።

የነቢዩ ትንቢት ግን አልቀረምና ታላቋ ነነዌ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ጠፍታለች። ቅዱስ ዮናስ ግን በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሯል። ጠቅላላ እድሜውም መቶ ሰባ ዓመት ነው።

ዛሬ ያለን ሁላችን ሃገራችን ነነዌን ሕዝቦቿም ሕዝቦቻቸውን ከመሰልን ሰንብተናል። በእርግጥ እንደ ነነዌ እሳት አይዘንብብን ይሆናል። ግን የዘላለም እሳት ይጠብቀናል። ንስሐ ካልገባን የሚመጣብን ቅጣት የሚከፋ ይሆናል።

አምላከ ቅዱስ ዮናስ እድሜ ለንስሐ፤ ዘመን ለፍስሐ አይንሳን። ጾሙንም የበረከት ያድርግልን።

"ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል። ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል። በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና። እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።"
(ማቴ ፲፪፥፴፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ለሃይማኖቴ አንገቴን እሰጣለሁ!

እንኳን ለጌታችን አማኑኤል ክርስቶስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ተአምራተ እግዚእ <3

"ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል። መሠረታዊ መልእክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው። ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ) ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል።

ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው። ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ - ከሐሌ ኩሉ - ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው።

እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል። በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ፣ መና ሲያዘንሙ፣ ውኃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት።) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ፣ እሳትን ሲያዘንሙ፣ ሙታንን ሲያስነሱ (፩ ነገሥት) እንደ ነበር ይታወቃል።

እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል። በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል።
(ማቴ. ፲፥፰ ፤ ፲፯፥፳ ፣ ማር. ፲፮፥፲፯ ፣ ሉቃ. ፲፥፲፯ ፣ ዮሐ. ፲፬፥፲፪)

እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል።
(ሐዋ. ፫፥፮ ፤ ፭፥፩ ፤ ፭፥፲፪ ፤ ፰፥፮ ፤ ፱፥፴፫-፵፫ ፣ ፲፬፥፰ ፤ ፲፱፥፲፩)

ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል። እያንዳንዱ ግን ቢጻፍ ዓለም ለራሷ ባልበቃች ነበር። ከእነዚህ መካከልም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህች ዕለት በሰባት እንጀራ እና በጥቂት ዓሣ ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨምር አራት ሺህ ሰዎችን በቸርነቱ አበርክቶ አጥግቧል። ደቀ መዛሙርቱም ሰባት ቅርጫት ማዕድ አንስተዋል።

ጌታችን በከሃሊነቱ የተራቡትን ሲያጠግብ እንዲሁ አይደለም። በጊዜው የነበሩ አይሁድ ጠማሞች ነበሩና እነርሱን ምላሽ በሚያሳጣ መንገድ ነበር እንጂ። አይሁድ ላለማመን ብዙ ጥረት ነበራቸውና።

በዚህች ዕለትም እንጀራውን አበርክቶ ሲያበላቸው፦
፩.ጊዜው አመሻሽ ላይ ነበር። ምክንያቱም ጧት ላይ ቢሆን ከቤታችን የበላነው ሳይጐድል ብለው ከማመን ይርቁ ነበርና።
፪.ከውኃ ዳር አድርጐታል። መታጠቢያ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ።
፫.ሳር የበዛበት ቦታ ላይ አድርጐታ። ምክንያቱም መቀመጫ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ።
፬.ከከተማ አርቆ ምድረ በዳ ላይ አድርጐታል። ያማ ባይሆን "ፈጣን ፈጣን ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው እየገዙ አቀረቡለት።" ባሉ ነበርና።

ለመድኃኒታችን ክርስቶስ አምልኮና ምስጋና ይሁን!
አማኑኤል አምላካችን ጣዕመ ፍቅሩን ያሳድርብን።

ጥር ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሰማዕት (ስለ ሃይማኖት ሰባት ጊዜ ሙቶ የተነሳ፣ ሰባት አክሊል የወረደለት)
፪.ቅዱስ አካውህ መነኮስ
፫.ስምንት መቶ ሰማዕታት
፬.ቅዱስ ዮሴፍ አይሁዳዊ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፭.ቅድስት ሳቤላ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባቶቻችን አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ
፪.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ

"ጌታ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ 'ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስከ አሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ። በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም።' አላቸው።
ደቀ መዛሙርቱም 'ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?' አሉት። ጌታ ኢየሱስም 'ስንት እንጀራ አላችሁ?' አላቸው። እነርሱም 'ሰባት ጥቂትም ትንሽ ዓሣ' አሉት።
ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ። ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በሉና ጠገቡ። የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሱ። የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ።"
(ማቴ ፲፭፥፴፪-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አረጋውያን ሰማዕታት <3

ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው። ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል። ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው።

ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል። የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው። "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው።

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ። ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም።

እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ። የሚረግሟችሁን መርቁ። ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ።" ብሎናልና።
(ማቴ. ፭፥፵፬)
ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚሆንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል።

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል። የቀደሙ ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና።

የእነዚህ ሰማዕታት ቁጥራቸው አርባ ዘጠኝ ሲሆን አባ ቢስዱራ የሚባል ጻድቅ ሰው ሃምሳኛ ሁኖ ይመራቸው ነበር። መኖሪያቸው ገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) ሆኖ ዘመኑ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበር።

ሃምሳውም ሙሉ ዘመናቸውን በምናኔና በቅድስና ፈጽመው በስተእርጅና ደግሞ ሰማዕትነት መጣላቸው። በ፬፻፴ዎቹ ዓ.ም አካባቢ የዚያን ጊዜ በርበር ይባሉ የነበሩት አረማውያኑ (የዛሬዎቹ አሕዛብ አባቶች) "ሃይማኖት ካዱ።" እያሉ ሰይፍን መዘዙባቸው።

በጊዜው አባ ቢስዱራ በማረፉ ኃላፊነቱን የወሰዱት አባ ዮሐንስ ከአርባ ስምንቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ተስማምተው በበርበር እጅ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። ከንጉሥ ቴዎዶስዮስ (ትንሹ) ተልኮ የነበረ አንድ ክርስቲያንም በፍቅረ ክርስቶስ ተስቦ ከወጣት ልጁ ጋር ተሰይፏል። የብርሃን አክሊልም ለሃምሳ አንዱም ወርዷል።

አምላከ ቅዱሳን ከተከፈተ ገነት፣ ከተነጠፈ ዕረፍት በቸርነቱ ያድርሰን።

ጥር ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት (ግብጽ ገዳመ አስቄጥስ ውስጥ)
፪.ቅድስት አንስጣስያ (በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከቁስጥንጥንያ ወደ ግብጽ ወርዳ ንግሥናን ንቃ በበርሃ ስትጋደል የኖረች ቅድስት
እናት ናት።)
፫.ቅዱስ ዮሴፍ (መፍቀሬ ነዳያን)
፬.አባ ጽሕማ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ኢትዮጵያዊ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ
ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን።' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ ፰፥፴፭-፴፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር) ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ መርቆሬዎስ ኃያል <3

ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት። ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው።

ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት "ካልዕ (ሁለተኛው) ሊቀ ሰማዕታት" ሲሉ ይገልጹታል።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር "አሮስ" የሚሉት ሰው ይኖር ነበር። ሚስቱ ደም ግባት የሠመረላት እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር።

አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ። እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ። የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል "እንስሳ ተያዘልን።" ብለው ሲሯሯጡ ዓይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው። ሁለት ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ውስጥ ተይዘው ነበር።

እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው። ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል። ግን እጅግ ግዙፍ፣ ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ፣ ወገባቸው እንደ ሰው፣ ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት የሚመስል ነው።

እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም። አንበሳና ነብርን እንኳ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል። ዓይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም። ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ። ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት። አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው።

"ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት።" አላቸው። ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው። በዚህ ጊዜ ሁለቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት። አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶ ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት።

ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች። ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት። ትርጉሙም "መፍቀሬ አብ - የአብ ወዳጅ" ማለት ነው። ከዚያም አሮስ ሚስቱን፣ ልጁንና ሁለቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ ተጠመቀ።

አበው ካህናት እሱን "ኖኅ"፣ ሚስቱን "ታቦት"፣ ልጁን ደግሞ "መርቆሬዎስ" ሲሉ ሰየሟቸው። መርቆሬዎስ ማለትም "ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ - የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው።

ከዚያም ደስ እያላቸው፣ ክርስቶስን እያመለኩ፣ ነዳያንን እያሰቡ፣ ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ። ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ "ካላመጣሃቸው" አለው። ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ።

ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው። በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር። አንድ ጊዜ ግን ሁለቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው። ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል "እንቢ" በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ።

በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ። ንጉሡ ደግሞ ታቦትን "ላግባሽ" ስላላት የአምስት ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች። በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው።

እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር። በኋላ ግን በሕፃኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው። በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው። በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ።

በዚያም ቤተ ክርስቲያንን አንጾ፣ ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጐ ኖኅ ለዓመታት ኖረ። ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ። እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት።

በጦርነት እጅግ ኃያል በሰው ዘንድ ፍጹም ተወዳጅ የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ። ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምዕመናን ላይ ሞት ታወጀ። በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግሥት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸው ዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ።

ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ። ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው።

በማግስቱም "ምን ይሻላል?" ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ "እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻየን እቋቋማቸዋለሁ።" ቢል ሳቁበት።

እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው።) ተጭኖ በርበሮችን "ጠብ ይቅርባችሁ፤ በሰላም ሒዱ።" ቢላቸው ተሳለቁበት። ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ። ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኳ የተረፈ አልነበረም።

ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ። ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ "ድሉ የጣዖቶቼ የነ አጵሎን ነው።" በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ።

በሦስተኛው ቀንም "ለጣዖት ሠዋ።" የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ። ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ። የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው።

"ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ - ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ ለጥፋት ይሁንህ።" ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው። ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው።

ያም አልበቃ ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው።
ለዚያ ነው ሊቃውንት፦
"አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም።" ያሉት።

ከዚያም ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት። ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ፣ በግርፋት፣ በእሳት፣ በስለትም አሰቃየው። በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው። በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር ፳፭ ቀን አንገቱን ሰይፈውታል።

እርሱ ካረፈ በኋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኳል። አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል። ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ፪፻ ዓ/ም እንደ ተወለደ በ፪፻፳ ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ፪፻፳፭ ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል።
ሰማዕቱ በዚህች ዕለት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖችን ያሰቃይና ይገድል የነበረውን ዑልያኖስን ያጠፋበት መታሠቢያ ይከበራል።
የቅዱሱ ክብር ታላቅ ነው።

አምላከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በከበረ ቃል ኪዳኑ ይጠብቀን። ከርስቱም አያናውጠን። ከበረከቱም ይክፈለን።
ቸሩ እግዚአብሔር እድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍሥሃ አይንሳን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ከወርቅና ከብር ይልቅ ሞገሱ የሚበልጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረሱ እኛን ለመርዳት ይምጣ፤ ይመላለስም።"
(ስብሐተ ፍቁር ዘጊዮርጊስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ እና ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ <3

ይህ ቅዱስ ሐዋርያ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን መብራት ነው። ወደ ክርስትና የመጣው በ፵ዎቹ ዓ.ም አካባቢ ሲሆን አሳምኖ ለቅድስና ያበቃው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው።

በጊዜውም በነበረው ትጋትና ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል። ሆዱንም እጅግ ያመው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ሲጠራው "የምወድህ ልጄ" እያለ ነበር። በኤፌሶንም ጵጵስናን ሹሞ ሁለት መልእክታትን ልኮለታል። ቅዱስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት አገልግሎ በሰማዕትነት ዐርፏል።

ከሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ በረከትን እንሳተፍ ዘንድ ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ጢሞቴዎስ ከላካቸው መልእክቶች ጥቂት እናንብብ።

<3 ቴዎዶስዮስ <3

በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ። ሰማዕታትም፣ ጻድቃንም፣ ሊቃውንትም፣ ነገሥታትም ተጠርተውበታልና። ዛሬ የምናከብረውም ቴዎዶስዮስ ዘየዓቢ (ታላቁ) የሚባል ሲሆን ይህን የምንለው ከትንሹ ቴዎዶስዮስ (የልጅ ልጁ ነው።) ለመለየት ነው።

ታላቁ ቴዎዶስዮስ በሮም የነገሠው በ፫፻፸ ዓ.ም አካባቢ ሲሆን ከነ ቤተሰቡ ክርስቲያን ነበር። እነዚህ ነገሮቹ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን እንዲታሰብ አድርጐታል፦
፩.በዓለም ታሪክ ክርስትና በሮም ግዛት ሁሉ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አውጇል።
፪.የቤተክርስቲያንን ትልቁን ሁለተኛ ጉባኤ ቁስጥንጥንያን በ፫፻፹፩ (፫፻፸፫) ዓ.ም አሰናድቷል።
፫.ከበጐነቱ የተነሳ የተቀደሱ ልጆችን አፍርቷል። ሙሽራው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ፣ ቅዱስ አኖሬዎስ፣ ቅዱስ አርቃዴዎስ እና ቅድስት ታኦድራ ልጆቹ ሲሆኑ አቡነ ኪሮስ ትንሽ ወንድሙ ናቸው።

ጻድቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ በ፫፻፺ ዓ.ም አካባቢ ዐርፏል።

አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል ይማረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ጥር ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጢሞቴዎስ (ሐዋርያና ሰማዕት - የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር)
፪.ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ (ዘቁስጥንጥንያ)
፫.ቅዱስ ጌርሎስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
፭.ቅዱስ አትናስዮስ ሰማዕት (ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተአምራቱ አሳምኖ ያስጠመቀው)
፮.አቡነ ጊዮርጊስ ዘዋሸራ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
፬.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭.አባ ሳሙኤል
፮.አባ ስምዖን
፯.አባ ገብርኤል

"መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ።
ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።"
(፩ጢሞ ፩፥፩-፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ኮከበ ገዳም አባ እንጦንስ እና ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ እንጦንስ <3

በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ/ዐቢይ/THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው። አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን።

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው። በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል። ሕይወቱ በጐላ በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው።

ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ፣ እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል።

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለአርባ ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል፤ አስተምሯል። በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት።

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። አኗኗራቸውም በቡድንም በነጠላም ሊሆን ይችላል።

ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው። ይህም ሲያያዝ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደረሰ። በዚህ ዘመን ግን አባ ጳውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይህንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው። ለሰማንያ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ። ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ።

ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት። በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ። ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ።

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል። ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል።

አባ እንጦንስ የመነኮሳት ሁሉ አባታቸው ለገዳማውያን ሁሉም ሞገሳቸው ናቸው። እንዲያውም ብዙ ጊዜ "ኮከበ ገዳም፣ ማኅቶተ ገድል (የበርሃው ኮከብ፣ የተጋድሎ መብራት)" ተብለውም ይጠራሉ።

ቤተ ክርስቲያን ለጀማሪዎች ትልቅ ትኩረት ትሰጣለች።
ለምሳሌ፦ አባ ጳውሊን (የካቲት ፪ የሚከበሩ) ለብሕትውና መሠረትን ስለ ጣሉ "አበ ባሕታውያን" ብላ ታከብራለች። አባ እንጦንስን ደግሞ "አበ መነኮሳት (የመነኮሳት አባት) ቀዳሚሆሙ ለመነኮሳት (ለመነኮሳት ቀዳሚና ጀማሪ) ስትል ትጠራቸዋለች።

አባ እንጦንስ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚነሱ ቅዱሳን መነኮሳት ሁሉ መንገድን ይጠርጉ ዘንድ ብዙ መከራን በትዕግስትና በአኮቴት ተቀብለዋል። ላለፉት አንድ ሺህ ሰባት መቶ ዓመታት እንደ ሻማ እየቀለጡ ያበሩ አበው ቅዱሳን ሁሉ የአባ እንጦንስ ልጆች ናቸው።

ከምጥ የከፋ የዲያብሎስ ፈተናን ተቀብለው ከመንፈሳዊ አብራካቸው ቅዱሳኑን ወልደዋል። የመነኮሳት አለቃ የሆኑትን ታላቁን መቃርዮስን ጨምሮ በርካቶችን አመንኩሰው ለቅድስና አብቅተዋል።

አባ እንጦንስ ግብጻዊ ሲሆኑ የተወለዱት አቅማን በምትባል ቦታ አካባቢ ነው። ጊዜውም በ፪፻፶፪ ዓ.ም ነው። የተባረኩ ወላጆች ለቅዱሱ እንጦንስና አስከትለው ለወለዷት ሴት ልጃቸው አስቀድመው ፍቅረ ክርስቶስን አስከትለውም ሃብት ንብረታቸውን አውርሰው ዐርፈዋል።

በዚህ ጊዜ የአባ እንጦንስ እድሜ አፍላ ወጣትነት ላይ ነበር። በልጅነት ጊዜአቸውም አባ እንጦንስን ሲስቁ፣ ሲጫወቱ፣ አልያም ሲቀልዱ አየሁ የሚል ሰው አልነበረም። ፍጹም ቁም ነገረኛና ታዛዥ በዚያ ላይም አስተዋይ ነበሩና ሙሉ ጊዜአቸውንም ከቅዱስ ቃሉ በመመገብ፣ በትምህርትና በማስቀደስ ያሳልፉ ነበር።

ዘወትርም ዜና ሐዋርያትን እያነበቡ በመንፈሳዊ ቅናት ይቃጠሉ ነበር። በጊዜው የምናኔ ሕይወት ጐልቶ ባለ መገለጡ አባ እንጦንስ የሚያደርጉት ይጨንቃቸው ነበር። ሲጸልዩም "አበው ሐዋርያት ይህንን ክፉ ዓለም ንቃችሁ ጌታችሁን የተከተላችሁበት ጥበብ እንደ ምን ያለ ነው!" እያሉ ይደነቁ ነበር። መሻታቸውን ያወቀ ጌታም ምሥጢርን ገለጠላቸው።

አንድ ቀን በቅዳሴ ላይ ወንጌል ሲነበብ ካህኑ ስለ ምናኔ የሚጠቅሰውን ክፍል አነበበ። ለአንድ ባለ ጠጋ ሕግጋትን ከነገረው በኋላ "ፍጹም ልትሆን ከወደድክስ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ተከተለኝ።" (ማር. ፲፥፲፯) የሚለውን ጥቅስ ሲሰሙ ተገርመው "ጌታ ሆይ! ይህንን የተናገርኸው ለእኔ ነው።" ሲሉ አሰቡ። በቀጥታም ሃብታቸውን ለአካባቢው ሰው አካፍለው እኅታቸውን ከደናግል ማኅበር ደምረው እርሳቸው ወደ ዱር ሔዱ።

ከዚህች ቀን ጀምረው አባ እንጦንስ ከሰማንያ እስከ መቶ ለሚደርሱ ዓመታት ከአጋንንት ጋር በጦርነት ኖሩ። በንጹሕ አምልኮታቸውና በቅድስናቸው የቀና ጠላት ሰይጣን በብዙ ጐዳና ፈተናቸው። አቅም ቢያጥረው አራዊትን መስሎ ታገላቸው።

በዚህ አልሳካ ቢለው የእሳት ሰንሰለትን አምጥቶ ገረፋቸው። በሞትና በሕይወት መካከል ጥሏቸው ሔደ። ወድቀው ያገኟቸው ሰዎች ለዘመዶቻቸው ሰጥተዋቸው አገገሙ። ልክ ሲነቁ ግን ፈጥነው ወደ በርሃ ተመለሱ።

ሰይጣን በርሃው የቅዱሳን ማደሪያ እንዳይሆን ሰግቷልና ጨክኖ ታገላቸው። ግን አልቻላቸውምና ተረታ። አምላከ ኃያላን ክርስቶስ ከቅዱሱ ጋር ነበርና። ከዚህ በኋላ ግን ጸጋው በዝቶላቸው ድውያንን የሚፈውሱና ሰይጣን የማይቀርባቸው ሰው ሆኑ።

በረዥም ዘመነ ቅድስናቸውም፦
፩.ብዙ አርድእትን ከመላው ዓለም ሰብስበው አስተምረው ምናኔን ከግብጽ ማዶ በመላው ዓለም አስፋፉ።
፪.በደመና እየተጫኑ ብዙ አሕጉራትንም እየዞሩ ሰበኩ። በዚህም አሕዛብን ወደ እምነት ኃጥአንን ወደ ንስሐ መለሱ።
፫.ጊዜው ዘመነ ሰማዕታት ነበርና ወደ አደባባይ ሒደው ከሃዲዎችን ገሠጹ። ማንም ደፍሮ ግን አልገደላቸውም።
እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን እየሠሩ በቅዱስ ሚካኤል እጅ መነኮሱ። እርሳቸውም ብዙዎችን አመነኮሱ። አርጅተው እንኳ ከተጋድሎ ያላረፉት አባታችን የጣመ ነገር ቀምሰው ገላቸውን ታጥበው አያውቁም። በ፫፻፸፪ ዓ.ም በዚህች ቀን ሲያርፉም ዕድሜአቸው መቶ ሃያ ደርሶ ነበር።

የአባ እንጦንስን በዓል ለማክበር የምትሹ ቤተ ክርስቲያናቸው ጎንደር ከተማ ከቀሃ ኢየሱስ በላይ ይገኛል።

ለአባታችን እንጦንዮስ /እንጦንስ/ እንጦኒ ክብር ይገባል!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ድንግል ሆይ! ነደ እሳት የማያቃጥላት በነበልባል ያጌጥሽ ዕፅ ነሽ። በጭንጫ ላይ በታነፀ ፎቅ ለመኖር እችል ዘንድ በዕውቀት ከፍ ከፍ አድርጊኝ፤ እንዳልወድቅም ደግፊኝ።"
(መልክአ ማርያም)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን አባቶቻችን ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ፣ ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት እና አባ ኤስድሮስ ገዳማዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ <3

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም። "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው፣ ልዑክ፣ የተላከ፣ የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው። በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፦
የፍጥረታት ሁሉ ጌታ የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ አድጐ፣ ተጠምቆ፣ ጾሞ፣ ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር።

ከተከተሉት የአምስት ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት መረጠ።
እኒህም
፩.ጴጥሮስ የተባለ ስምኦን
፪.እንድርያስ (ወንድሙ)
፫.ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
፬.ዮሐንስ (ወንድሙ)
፭.ፊልጶስ
፮.በርተሎሜዎስ
፯.ቶማስ
፰.ማቴዎስ
፱.ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
፲.ታዴዎስ (ልብድዮስ)
፲፩.ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና
፲፪.ማትያስ (በይሁዳ የተተካ) ናቸው።
(ማቴ. ፲፥፩)

እነዚህን አሥራ ሁለት አርድእቱን ከጠራ በኋላ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር። ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር።

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በኋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው። ለዓለም እረኞች የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ። እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው።
(ማቴ. ፲፥፲፮፣ ዮሐ. ፲፮፥፴፫)
በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው።
(ማቴ. ፲፱፥፳፰)

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ። "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።"
(ማቴ. ፲፰፥፲፰)
"ይቅር ያላችኋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፤ ያላላችኋቸው ግን አይቀርላቸውም።"
(ዮሐ. ፳፥፳፫)

የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. ፲፮፥፲፱)፣ እረኝነትን (ዮሐ. ፳፩፥፲፭) ተቀበሉ። ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው፣ የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. ፭፥፲፫) አላቸው። ወንድሞቹም ተባሉ።
(ዮሐ. ፯፥፭)
ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው።

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ። ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሣኤ ተመለከቱ። እጆቹን እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ።

ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓት ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው ጌታ ሊቀ ጵጵስናን ሹሟቸው ዐረገ።

ለአሥር ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው። በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን ብርሃናውያን ሆኑ። ሰባ አንድ ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ ሦስት ሺህ ነፍሳትን ማረኩ።
(ሐዋ. ፪፥፵፩)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እስራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል። ከዚህ በኋላ ግን እንደ ትውፊቱ ዓለምን በእጣ ለአሥራ ሁለት ተካፈሏት።

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው። እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ።

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ፣ ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ። በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ። በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ፣ ለምጻሞችን አነጹ፣ እውራንን አበሩ፣ አንካሶችን አረቱ፣ ጐባጦችን አቀኑ፣ ሙታንንም አስነሱ። እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ።

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ፣ ቆዳቸው ተገፈፈ፣ በምጣድ ተጠበሱ፣ ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ። ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ። ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና፤ ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን። "አባቶቻችን፣ መምህሮቻችን፣ ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን።

ከእነዚህ አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ (የእልፍዮስ ልጅ) ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ (ማቴ. ፲፥፩) ብዙ አሕጉር አስተምሮ በዚህ ቀን በሰማዕትነት ወደ ፈጣሪው ሔዷል። የተሰዋው በድንጋይ ተወግሮ ሲሆን ገዳዮቹ ደግሞ የዘመኑ አይሁድ ናቸው።

<3 ቅዱስ ዮስጦስ <3

ቅዱስ ዮስጦስ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ምድራዊ የንግሥና ዙፋንን ንቆ በክርስቶስ ስም በሰማዕትነት ከሚስቱ ቅድስት ታውክልያና ከአንድ ልጁ ቅዱስ አቦሊ ጋር ሰማያዊ ክብርን ተቀዳጅቷል።

<3 አባ ኤስድሮስ ገዳማዊ <3

አባ ኤስድሮስ ግብጻዊ ሲሆኑ ሹመትን ጠልተው ፈርማ በሚባል ገዳም ለስልሳ ዓመታት በበርሃ ውስጥ ከአሥራ ስምንት ሺህ በላይ ድርሳናትን ጽፈዋል። ይህም በዓለም ታሪክ ብዙ መጻሕፍትን በመጻፍ ቀዳሚው ያደርጋቸዋል። ከድርሳናቱ መካከል ሁለት ሺህ ያህሉ ዛሬም ድረስ በግብጽ በርሃ ውስጥ ይገኛሉ።

አምላከ ቅዱሳን ቸርነቱን ምሕረቱን ያብዛልን። በምልጃቸው ሃገራችንን ከክፉ ጠብቆ ከበረከታቸው ይክፈለን።

የካቲት ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፪.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት
፫.አባ ኤስድሮስ ጻድቅ (ዘሃገረ ፈርማ)
፬.አባ ፌሎ ሰማዕት
፭.ቅዱስ ስምዖን
፮.ቅዱስ ኒቆላዎስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፪.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፬.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
፭.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፮.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ

"ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ ይናፍቁአችኋል።
ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።"
(፪ቆሮ ፱፥፲፬)

"ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ።"
(ኤፌ ፭፥፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 በዓለ ስምዖን <3

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ጌታ በተወለደ በአርባ ቀኑ ራሱ የሠራውን ሕግ ይፈፅም ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል። እንደ ሥርዓቱም እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምና አገልጋዩዋ ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ የርግብ ግልገሎችና ዋኖስ አቅርበዋል።

ለሁለት መቶ ሰማንያ አራት ዓመታት የአዳኙን (የመሲሑን) መምጣት ይጠብቅ የነበረው አረጋዊው ስምዖን በዚህች ዕለት ስላየውና ስለታቀፈው ዕለቱ "በዓለ ስምዖን" ይባላል።
(ሉቃ. ፪፥፳፪)
ከዘጠኙ የጌታ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ከዓለም ፍጥረት በአምስት ሺህ ሁለት መቶ ዓመታት (ማለትም ከክርስቶስ ልደት ሦስት መቶ ዓመታት በፊት) በጥሊሞስ የሚሉት ንጉሥ በግሪክ ነገሠ።

በጊዜውም በኃይለኝነቱ ሁሉን አስገብሮት ነበርና "ዓለሙን እንደ ሰም አቅልጬ እንደ ገል ቀጥቅጬ ገዛሁት። ምን የቀረኝ ነገር አለ?" ሲል ተናገረ። ባሮቹም "አንድ ነገር ቀርቶሃል። በምድረ እስራኤል ጥበብን የተሞሉ አርባ ስድስት መጻሕፍት አሉ። እነርሱን አስተርጉም።" አሉት።

ያን ጊዜ እስራኤላውያንን አስገብሯቸው ነበርና አርባ ስድስቱን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከሰባ ሁለት ምሑራን (ተርጓሚዎች) ጋር እንዲያመጡለት አዛዦቹን ላከ። እነርሱም አርባ ስድስቱን መጻሕፍተ ብሉይ ኪዳን ከሰባ ሁለት ምሑራን ጋር አመጡለት።

አይሁድ ክፋተኞች መሆናቸውን ሰምቷልና ሠላሳ ስድስት ድንኳን አዘጋጅቶ ጥንድ ጥንድ ሆነው እንዲሠሩ ሲተረጉሙ እንዳይመካከሩ ሠላሳ ስድስት ጠባቂዎችን ሾመባቸው። ይህ ነገር ለጊዜው ከንጉሡ ቢመስልም ጥበቡ ግን ከእግዚአብሔር ነው።

ምክንያቱም በጊዜ ሒደት መጻሕፍተ ብሉያት በአደጋ እንደሚጠፉ ያውቃልና ሳይበረዙ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች (ለእኛ) እንዲደርሱ ነው። ስለዚህም ከክርስቶስ ልደት ሁለት መቶ ሰማንያ አራት ዓመታት በፊት አርባ ስድስቱም (ሁሉም) መጻሕፍተ ብሉያት ከዕብራይስጥ በሰባው ሊቃናት አማካኝነት ወደ ጽርዕ ልሳን ተተረጐሙ።
(በእርግጥ ከዚያ አስቀድሞ መጻሕፍት (ብሉያት) ወደ ሃገራችን መምጣቸውና ወደ ግዕዝ ልሳን መተርጐማቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው!)

ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ ከሰባው ሊቃናት መካከል በእድሜው አረጋዊ የሆነ (እንደ ትውፊቱ ከሆነ ሁለት መቶ አሥራ ስድስት ዓመት የሆነው) ስምዖን የሚሉት ምሑረ ኦሪት ነበር። በፈቃደ እግዚአብሔር ለእርሱ መጽሐፈ ትንቢተ ኢሳይያስ ደርሶት እየተረጐመ ምዕራፍ ሰባት ላይ ደረሰ።

ቁጥር ሰባት ላይ ሲደርስ ግን "ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ" የሚል አይቶ "አሁን እንኳን የአሕዛብ ንጉሥ የእስራኤልስ ቢሆን ድንግል በድንግልና ጸንሳ ትወልዳለች ብለው እንዴት ያምነኛል!" ሲል አሰበ። "በዚያውስ ላይ ኢሳይያስ በምናሴ የተገደለው ስለዚህ አይደል!" ብሎ ቃሉን ሊለውጠው ወሰነ።

አመሻሽ ላይም "ድንግል" የሚለውን "ወለት (ሴት ልጅ)' ብሎ ቀየረው። እርሱ ሲያንቀላፋ ቅዱስ መልአክ ወርዶ "ድንግል" ብሎ አስተካከለው። ከእንቅልፉ ሲነቃ ግራ ተጋብቶ እንደ ገና ፍቆ ቀየረው።

አሁንም መልአኩ "ድንግል" ሲል ቀየረበት። ሦስት ጊዜ እንዲህ ከሆነ በኋላ ግን መልአኩ ተገልጦ ገሰጸው። በዚያውም ላይ "ይህችን ድንግልና መሲሑን ልጇን ሳታየውና ሳትታቀፈው ሞትን አታይም።" ብሎት ተሰወረው። አረጋዊ ስምዖን ከዚያች ዕለት በኋላ የመድኅን ክርስቶስን መምጣት ሲጠብቅ ለሁለት መቶ ሰማንያ አራት ዓመታት የአልጋ ቁራኛ ሁኖ ኖረ፤ አካሉም አለቀ።

ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በሆነበት በዚያ ሰሞን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ።

ሕግን የሠራ ጌታ እርሱ "ፈጻሜ ሕግ" ይባል ዘንድ የርግብ ግልገሎችን (ዋኖሶችን) ይዘው በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገቡት። በዚህች ቀንም ቅዱስ መልአክ መጥቶ ቅዱስ ስምዖንን ከአልጋው ቀሰቀሰው። ተስፋ የሚያደርገው አዳኙ (መሲሑ) እንደ መጣም ነገረው።

ይህን ጊዜ አረጋዊው አካሉ ታድሶ እንደ ሠላሳ ዓመት ወጣት እመር ብሎ ከአልጋው ተነሳ። እንደ በቅሎ እየሠገረም ወደ መቅደስ ወጣ። በዚያ መሲሑን (ፈጣሪውን) ሲመለከት እንደ እንቦሳ ዘለለ። ቀረብ ብሎም ሕፃን ጌታን ከድንግል እናቱ እጅ ተቀበለው።

ከደስታው ብዛት የተነሳም "ይእዜ ትስዕሮ ለገብርከ በሰላም እግዚኦ በከመ አዘዝከ - አቤቱ ባሪያህን እንደ ቃልህ በሰላም አሰናብተው።" ሲል ጸለየ። ትንቢትንም ተናገረ። በዚያችው ዕለትም ዐርፎ ተቀበረ።

<3 ሐና ነቢይት <3

ዳግመኛ በዚህች ቀን አረጋዊቷን ነቢይት ቅድስት ሐናን እናስባለን። ይህች ቅድስት ትውልዷ ከነገደ አሴር ሲሆን አባቷ ፋኑኤል ይባላል። በትውፊት ትምህርት ሐና የተዳረችው በልጅነቷ (በአሥራ ሁለት ዓመቷ) ነው። ለሰባት ዓመታት ከልጅነት ባሏ ጋር ኖራ ዕድሜዋ አሥራ ዘጠኝ ሲደርስ ሞተባት።

እንደ እስራኤል ልማድ ሌላ እንድታገባ ብትጠየቅም "እንቢ" ብላ መበለት ሆነች። ራሷንም ለእግዚአብሔር አሳልፋ ሰጠች። በቤተ መቅደስም ለሰማንያ አራት ዓመታት ለፈጣሪዋ ተገዛች። ፈጽማ ትጸልይና ትጾም ነበርና በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውጪውን አልተመለከተችም።

ለእርሷ መቶ ሦስት ዓመት ሲሆን መድኃኒታችን ተወለደ። በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ተመልክታም ጌታን ባረከች። ደስ እያላትም ትንቢትን ተናገረች። ወደ ቤቷ ገብታም ነፍሷን ሰጠች።
(ሉቃ. ፪፥፴፮-፴፰)

አረጋዊ ስምዖንን ከድካም አልጋ ያነሳ አምላከ ቅዱሳን እኛንም ድካመ ነፍስን ከሚያመጣ የበደል መኝታ በቸርነቱ ያንሳን።

ቸሩ መድኃኒታችን ተርፎ ከሚቀረው ዘመን ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍሥሐ አይንሳን። ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን።

የካቲት ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ስምዖን አረጋዊ
፪.ቅድስት ሐና ነቢይት (የፋኑኤል ልጅ)
፫.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ እግዝእት
፬.አባ ኤልያስ ገዳማዊ (በትህትና ያጌጠ ቅዱስ ሰው)
፭.አቡነ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ
፮.አቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ
፫.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፬.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፭.አቡነ ኪሮስ
፮.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን

"እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ጌታ ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው። እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ 'ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ። ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና። ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።' ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባለው ነገር ይደነቁ ነበር።"
(ሉቃ ፪፥፳፯-፴፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእናታችን ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት እና ቅዱስ አቡሊዲስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅድስት ማርያም <3

ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለን በስምዖን ቤት የመድኃኔ ዓለምን እግር በእንባዋ አጥባለች። በጸጉሯም አብሳ የሦስት መቶ ብር ሽቱ ቀብታዋለች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የቀደመ ኃጢአቷን ይቅር ብሎ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ደምሯታል።
(ሉቃ. ፯፥፴፮-፶)

ስለዚህች ቅድስት ሙሉ ታሪክ፦
፩.ትርጓሜ ወንጌልን
፪.ተአምረ ኢየሱስን
፫.ስንክሳርንና
፬.መጽሐፈ ግንዘትን በማንበብ ማግኘት ይቻላል።

እንተ ዕፍረት (ባለ ሽቱዋ ማለት ነው።) ማርያም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን (በዘመነ ስብከቱ) የነበረችና ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ሴት ነበረች። ግን መልክ የመልካም ነገሮች ምንጭ ሲሆን አይታይም።

በመልካቸው ማማር የጠፉና ያጠፉ ብዙ ሴቶችን ዓለማችን አስተናግዳለች። ከክሊዎፓትራ እስከ ዘመናችን "ሞዴል" ነን ባዮች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ጸጋ የሰይጣን መደሰቻ የገሃነም መንገድ አድርገውት ማየት (መስማት) እጅግ ያሳዝናል።

በአንጻሩ ደግሞ ብዙዎችን ያስደመመ መልካቸውን ንቀው ሰማያዊ ሙሽርነትን የመረጡትን ቅዱሳቱን አርሴማን፣ ቴክላን፣ ጤቅላን፣ መሪናን፣ ጣጡስን፣ ሔራኒን፣ ኢራኒን፣ አትናስያን፣ ሶፍያን፣ ኢላርያን ስናስብ ደስ ይለናል። ዛሬም ጌታ በሚያውቀው ብዙ እናቶቻችን (እኅቶቻችንም) ተመሳሳዩን በጐ ጐዳና መርጠው እየተጓዙ መሆኑን እናውቃለን።

ቅድስት ማርያምም ከፈጣሪዋ በተሰጣት ቁንጅና ክፋትን ትሠራ ዘንድ ሰይጣን ሲያገብራት "እሺ" ብላ የእሱ ወጥመድ ልትሆን ተራመደች። ለዘመናትም ዓይነ ዘማ፣ ልበ ስስ የሆኑ ወንዶችን ወደ ኃጢአት ጐዳና ማረከች።

ለመልኳ ከነበራት ስስት የተነሳም ቶሎ ቶሎ ራሷን በመጽሔት (መስታውት ማለት ነው።) ትመለከት ነበር። መቼም አምላካችን ለሁሉም የመዳን ቀን ጥሪ አለውና (የሚያስተውለው ቢገኝ) ለማርያም ጥሪውን ላከላት። ጥሪው ግን በስብከት፣ በመዝሙር ወይም በመጽሐፍ አልነበረም።

እንዳስለመደች ውበቷን ለመመልከት መስታውት ፊት ቆማ የራሷን ጸጉር፣ ግንባር፣ ዓይን፣ አፍንጫ፣ ጥርስ እየተመለከተች ተደመመች። ወዲያው ግን ይህ አካል አፈር እንደሚበላው የሚያስብ ልቡና መንፈስ ቅዱስ አምጥቶባት በጣም አዘነች። የመኖር ተስፋዋ እንዳይቆረጥ ደግሞ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ዜና ሰማች።

መወሰን ነበረባትና ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ልትሔድ ቆረጠች። በአምላኳ ፊት የሚቀርቡም ሦስት ስጦታዎችን አዘጋጀች። ሰይጣን ሊያጣት አልፈለገምና ወደ ክርስቶስ እንዳትደርስ ብዙ መሰናክልን ፈጠረባት። ግን ውሳኔዋ የእውነት ነበርና እያሳፈረችው ወደ አምላኳ ገሰገሰች።

የስምዖን ዘለምጽ በረኞችም ሊያስቀሯት አልተቻላቸውም። ወደ ውስጥ ዘልቃ የያዘችውን ሁሉ ለመድኃኒታችን ሰዋች።
፩.ከውስጧ እንባዋን፣
፪.ከአካሏ ጸጉሯንና
፫.ከንብረቷ ውድ የሆነውን ሽቱ አቀረበች።

ብዙ ወዳለችና ብዙ ኃጢአቷ ተሠርዮ ቅድስት እናታችን ሆነች። ብዙ አዝማናትን ከሐዋርያት ጋር አገልግላም በዚህች ቀን ዐርፋለች።

<3 ቅዱስ አቡሊዲስ መምህረ ኩሉ ዓለም <3

የዓለም ሁሉ መምህር፣
ባለ ብዙ ድርሳንና ተግሣጽ፣
የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ፣
ሠላሳ ስምንት ሕግጋትን የደነገገ፣
ስለ ቀናች እምነት የተጋደለ፣
መራራ ሞትን በደስታ የተቀበለ፣
የቀደመችዋ ሮም ሊቀ ጳጳሳት የነበረና ሐዋርያትን የመሰለ አባት ነው።

በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ያበራው ይህን ኮከብ ካቶሊካውያን ክደውታል። እነርሱ "አቡሊዲስ የሚባል ጳጳስ አልነበረም።" ቢሉም ምክንያታቸው ግን ከሰይጣን ነው። ሃይማኖታቸውን ከመለወጣቸው ሁለት መቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት ስለተናገረባቸውና አንድ ባሕርይን ስላስተማረ መሆኑን ዓለም ያውቃል።

አባታችን ቅዱስ አቡሊዲስ የተገደለ የካቲት ፭ ቀን ሲሆን የካቲት ፮ ሥጋው የተገኘበት ነው።

አምላከ ቅዱሳን ከቅድስት ማርያም ንስሐዋን ከአባ አቡሊዲስ ምሥጢረ ቅድስናውን ያድለን።
ከበረከተ ቅዱሳን ይክፈለን።

የካቲት ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት
፪.የዓለም ሁሉ መምህር ቅዱስ አቡሊዲስ (ብዙ መንፈሳዊ ድርሳናትን የደረሰ ሊቀ ጳጳስና ሰማዕት)
፫.ቅዱሳን አቡቂርና ዮሐንስ (ሰማዕታት)
፬.ቅድስት አትናስያና ሦስቱ ሰማዕታት ልጆቿ (ቴዎድራ፣ ቴዎፍናና ቴዎዶክስያ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም። እርሷ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአቷ ተሰርዮላታል። ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። እርስዋንም 'ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል።' አላት። ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው 'ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማነው?' ይሉ ጀመር። ሴቲቱንም 'እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሒጂ።' አላት።"
(ሉቃ ፯፥፵፮-፶)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ አጋቦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አጋቦስ ሐዋርያ <3

ከሰባ ሁለቱ አርድዕት አንዱ የሆነው ቅዱሱ ሐዋርያ ሃብተ ትንቢት የተሠጠውና በዘመነ ሐዋርያት (በቀላውዴዎስ ቄሳር ጊዜ) በዓለም ላይ ከባድ ረሃብ እንደሚሆን ትንቢት የተናገረና በርካታ ክርስቲያኖችን ከረሃብና ከሞት የታደገ ትልቅ ሐዋርያ ነው።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)

በቅዱስ ጳውሎስ ላይ የሚደርሰውን መከራ በመናገሩም "ሐዋርያ ትንቢት" ተብሏል። በአገልግሎቱ ከአይሁድና ከአረማውያን ብዙዎችን ወደ ክርስትና በመሳቡ የተበሳጩ አይሁድም በዚህች ቀን ገድለውታል። በተቀደሰ ሥጋው (መቃብሩ) ላይ ብርሃን ሲወርድ ያየች አይሁዳዊት ሴትም በክርስቶስ አምና ተሰውታለች።

የአባታችን በረከት ይደርብን።

የካቲት ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አጋቦስ ነቢይ፣ ሐዋርያና ሰማዕት
፪.አባ ዘካርያስ ትሩፈ ምግባር

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ ወልደ ነጎድጓድ
፪.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫.ቅድስት ሶፊያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ

"በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ።
ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነስቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ። ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ።
ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ።
እንዲህም ደግሞ አደረጉ። በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት።"
(ሐዋ ፲፩፥፳፯-፴)

"ስለ እኛ ትጸልዩ ዘንድ ይገባችኋል። ለሁሉ መልካም ነገርን እንደምትወዱና እንደምትሹ እናምናለን።"
(ዕብ ፲፫፥፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

የካቲት ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (የባሕታውያን ሁሉ አባት)
፪.ቅዱስ አባ ለንጊኖስ ሊቀ ምኔት (ደብረ ዝጋግ)
፫.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ (የሃይማኖት ጠበቃ)
፬.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ
፭.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፮.አባ ሕርያቆስ ዘሐገረ ብሕንሳ

"የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ። ተፈተኑ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ፣ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ሰማዕትነት አያምልጠን!

እንኳን ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ እና ለመቶ ሃምሳው ቅዱሳን ሊቃውንት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕት <3

የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ነው።
ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት። ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ ፭ ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራእይ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት። በወለደችው ጊዜም በራእዩ መሠረት "ጴጥሮስ" አለችው።

ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተውት በሊቀ ጳጳሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ፣ ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ። ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ጴጥሮስን የግብጽ አሥራ ሰባተኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት።

ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር። ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር። ለአሥራ አራት ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ።

አርዮስን (ተማሪው ነበር።) አውግዞ ለየው። ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ። ብዙ ተአምራትንም ሠራ። በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ጵጵስናው ላይ አልተቀመጠም። በኋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ።

ሕዝቡ "ከእርሱ በፊት እኛን ግደሉን።" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ጴጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ። በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ። ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ። ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ። ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ።
የቅዱሳንን ዝክር ከማንበብ ባለፈ በስማቸው መጸለይ (ዘፀ. ፴፪፥፲፫) በምጽዋትም ማሰብ (ማቴ. ፲፥፵፩) ይገባል።

<3 መቶ ሃምሳ ቅዱሳን ሊቃውንት ጳጳሳት <3

በቁስጥንጥንያ ተሠብሥበው መናፍቃንን ያወገዙት፣ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን ያፀኑትና ጉባዔ ቁስጥንጥንያ በ፫፻፹፩ ዓ.ም ያደረጉት በዚህች ዕለት ነው።
ከወቅቱ ቅዱሳን ሊቃውንት መካከልም፦
ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ፣
ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ፣
ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪትና ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ይጠቀሳሉ።

የቅዱሳን አባቶቻችን በረከት ይደርብን።
ወርኀ የካቲትን ይባርክልን!

የካቲት ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
፪.መቶ ሃምሳ ቅዱሳን ሊቃውንት ጳጳሳት
፫.ታላቁ ቴዎዶስዮስ ጻድቅ (ንጉሠ ቁስጥንጥንያ)
፬.ሰማዕቱ አቡነ ሲኖዳ (ፍልሠታቸው)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለቅድስት ድንግል ማርያም እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ
፭.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት

"ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ..... እኔ አውቃለሁ።
ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።"
(ሐዋ ፳፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እኔን ከአንቺ የሚለየኝ የለም! - እናቴ ቤተ ክርስቲያን

እንኳን ለቅዱሳት አንስት ሶፍያ ወአዋልዲሃ፣ ኦርኒ ወማኅበራኒሃ እና ለሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅድስት ሶፍያና ልጆቿ <3

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታዋቂ ከሆኑ የእናቶቻችን ስሞች "ሶፍያ" ቀዳሚው ነው። ቃሉ በጥሬው ሲተረጐም "ጥበብ (ጥበበ ክርስቶስ) Wisdom of God" ማለት ነው። ከጻድቃንና ከሰማዕታት ወገን በዚህ ስም የተጠሩ እናቶች አሉ።

ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው በዕለቱ የምናስባት እናት ቁጥሯ ከሰማዕታት ነው። ዋናው ዘመነ ሰማዕታት ከመጀመሩ በፊት የነበረችው ቅድስት ሶፍያ ከሕግ ትዳር ሦስት ሴቶች ልጆችን አፍርታለች።

ስማቸውንም ጲስጢስ (ሃይማኖት)፣ አላጲስ (ተስፋ) እና አጋጲስ (ፍቅር) ስትል ሰይማቸዋለች። እንደሚገባም በሥርዓቱ አሳድጋ እድሜአቸው ዘጠኝ፣ አሥር እና አሥራ ሁለት ሲደርስ ለሰማያዊ ሙሽርነት አጭታቸዋለች።

በዘመኑ "ክርስቶስን ካዱ።" የሚል መሪ ተነስቶ ነበርና ቅዱሳቱ በመድኃኒታችን አምነው ጣዖትን ዘልፈው አንገታቸውን ሰጥተዋል። ክብረ ሰማዕትን ሃገረ ክርስቶስንም ወርሰዋል።

<3 ቅድስት ኦርኒ ሰማዕት <3

"ኦርኒ" ማለት በምሥራቃውያን ልሳን "ሰላም" ማለት ነው። ቅድስቲቱ አርበኛ የዘመነ ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን ፍሬ ስትሆን ተወልዳ ያደገችውም በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ነው።

ምንም ዛሬ ያለ ትውልድ ቢዘነጋት ቅድስት ኦርኒ ተወዳዳሪ የሌላት ሰማዕት፣ ሐዋርያዊት፣ ድንግል ናት። እርሷ ውበቷን፣ ንግሥናዋን፣ ክብሯን፣ ሃብቷን፣ ወጣትነቷንና ያላትን ሁሉ ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ሰውታለችና ክብርት ናት።

በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ቤተ መንግሥት የተወለደችው ቅድስት ኦርኒ እስከ ወጣትነቷ ድረስ ክርስቶስን ልታውቀው አልተቻላትም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ንጉሡ አባቷ ጣዖትን ማምለኩ ነበር።

ንግሥት እናቷ ምንም ክርስቲያን ብትሆንም ስለ ክርስትና ልትነግራት አልደፈረችም። ይህን ብታደርግ የሚደርስባትን መከራ ታውቃለችና። ግን ደግሞ ውስጥ ውስጡን ትጸልይላት ነበርና ፈጣሪ መንገዱን ሊከፍት ጀመረ።

መምለኬ ጣዖት አባቷ ሰው እንዳያያት ቤተ መንግሥት ሠርቶ፣ አሥራ ሁለት ሞግዚቶችን መድቦ ጣዖት ከፊቷ አቁሞ ለዘመናት ዘጋት። የሚገርመው ግን መልኳን እንዳያይ በበር ሆኖ የሚያስተምራት ፈላስፋ ተቀጥሮ ነበርና የዚህ ሰው ማንነቱ ነው።

መምለኬ ክርስቶስ ደግ ሰው ነበርና ፈሊጥን ይሻላት ገባ። በዚህ መካከል ቅድስት ኦርኒ ራእይን ታያለች። የቤቷ መስኮቶች ተከፍተው ሳሉ በስተምሥራቅ ነጭ ርግብ የዘይት (የወይራ) ዝንጣፊ ይዛ ገብታ ከማዕዷ ላይ ጥላው ወጣች።

እርሷን ተከትሎ ቁራ በምዕራብ ገባ። እባቡን ማዕዷ ላይ ጣለው። በሦስተኛው ደግሞ ንስር ገብቶ አክሊል ትቶላት ወጣ። ቅድስቲቱም እየገረማት አረጋዊ መምህሯን "ተርጉምልኝ" አለችው።
እርሱም፦
"ርግብ = ጥበብ (መንፈስ ቅዱስ)፣
ዘይት = ጥምቀት፣
ቁራ = ክፉ ንጉሥ፣
እባብ = መከራ፣
ንስር = ድል ነሺነት (ልዑላዊነት)፣
አክሊልም = ክብረ ሰማዕታት ነው።" ብሎ ተርጉሞ ክርስቲያን ሆና ይህ ሁሉ እንደሚደረግ ነግሮ ተሰናበታት።

እርሷም ስትጸልይ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አጽናናት። ያጠምቃትና ያስተምራት ዘንድም ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስን ልኮላታል። ሐዋርያውም የቤተ መንግሥቱን ግድግዳ ሰንጥቆ ገብቶ ለሰማያዊ ሙሽርነት የሚያበቃ ትምህርትና ጥምቀትን ሰጥቷት ሔዷል።

ቅድስት ኦርኒም የአባቷን ጣዖታት ቀጥቅጣ ሰብራ ከአባቷ ጋር ተጣላች። እርሱም "እገድላታለሁ" ብሎ በእንስሳት ጅራት ላይ ጸጉሯን ሲያስር እንስሶቹ ደንብረው እጁን ገንጥለው መሬት ላይ ጥለው ገደሉት። ቅድስት ኦርኒ ግን ጸሎት አድርሳ አባቷን ከሞት አስነሳችው፤ እጁንም ቀጠለችለት።

በዚህ ምክንያት በዚያች ዕለት ብቻ አባቷና ሠላሳ ሺህ የከተማው አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል። ቅድስት ኦርኒ ግን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ታጥቃ ክርስትናን ሰበከች፤ ብዙም ተሰቃየች። ንጉሡ ዳኬዎስ፣ ልጁና ሌሎች ሁለት ያህል ነገሥታት በእሳት፣ በአራዊት፣ በግርፋትና በጦር ፈትነዋታል።

እርሷ ግን ሁሉን በኃይለ ክርስቶስ ድል ነስታለች። ሙታም የተነሳችበት ጊዜ አለ። በመጨረሻም በዚህች ቀን ወደ ሰማያዊ ርስት (ገነት) ተመስጣለች። በዘመነ ስብከቷ ካሳመነቻቸው ባሻገር አሥራ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ለሰማዕትነት እንዲበቁም ምክንያት ሆናለች።

<3 ቅዱስ ጐርጐርዮስ ታኦሎጐስ <3

ቅዱሱ፦
የዘመነ ሊቃውንት ፍሬ፣
የእንዚናዙ ኤጲስ ቆጶስ፣
የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ፣
የጉባዔ ቁስጥንጥንያ (በ፫፻፹፩ ዓ.ም) ሦስተኛ ሊቀ መንበር፣
ባለ ብዙ ድርሳን፣
የቂሣርያ (ቀጰዶቅያ) ኮከብ፣
ብሩህ ገዳማዊና መልካም እረኛ የነበረ አባት ነው።
መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በጻፋቸው ብዙ መጻሕፍትና በስብከቱ ከሊቃውንት ወገን "ታኦ(ዎ)ሎጐስ" ተብሎ የተጠራ እርሱ ብቻ ነው። ትርጉሙም በግዕዙ "ነባቤ መለኮት" ማለት ነው። በአማርኛም "አንድነትን ሦስትነትን የተናገረ (ያመሠጠረ)" እንደ ማለት ነው። ቅዱሱ ዛሬ ዕረፍቱ ነው።

አምላከ ቅዱሳን ከበረከታቸው ይክፈለን።
በመጽናታቸውም ያጽናን።

እንዲህ ኃጢአታችን ጽዋዑን ሞልቶ በተረፈበት በዚህ ዘመን አንዲት ሰዓትም ውድ የሆነች የንስሐ ዕድሜ ናት። እግዚአብሔር ግን ደግ ነውና ይሔው ጥርን አስፈጸመን። ባይገባን ነው እንጂ በዚህች ወር ውስጥ ሚሊየኖች በደዌ የአልጋ ቁራኛ ሁነዋል።

ሚሊየኖችም ለንስሐ ሳይበቁ እንዲሁ አንቀላፍተዋል (ሙተዋል)። እስኪ እርሱ አምላካችን ቀሪውን ዘመን ደግሞ ለንስሐና ለመልካም ሥራ ባርኮ ይስጠን።

ወርኀ ጥርን በቸር ያስፈፀመ አምላከ ቅዱሳን ወርኀ የካቲትን እንዲባርክልን እንለምነው።

ጥር ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ሶፍያና ሦስቱ ሰማዕታት ልጆቿ (ጲስጢስ፣ አላጲስና አጋጲስ)
፪.ቅድስት ኦርኒ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬.አባ አክርስጥሮስ
፭.አምስቱ ደናግል ሰማዕታት (ጤቅላ፣ ማርያ፣ ማርታ፣ አበያና ዓመታ)
፮.ጻድቃነ ዴጌ (የተሠወሩበት)
፯.አባ ሚናስ ሊቀ ጳጳሳት
፰.አሥራ ሦስት ሺህ ሰማዕታት (የቅድስት ኦርኒ ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ
፪.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፫.አባ ሣሉሲ ክቡር

"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።"
(፩ጴጥ ፫፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ለሃይማኖቴ አንገቴን እሰጣለሁ!

እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃነ ዴጌ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጻድቃነ ዴጌ <3

እነዚህ ጻድቃን ኢትዮጵያውያን ባይሆኑም ያበሩት በሃገራችን ነው። ቅዱሳኑ በቁጥር ሦስት ሺህ ሲሆኑ በዜግነት ሮማውያን ናቸው። ከሺህ አዝማናት በፊት ከሮም ግዛት ተሰባስበው እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ (አክሱም) መጥተዋል።

ቀጥለውም እዚያው አካባቢ ወደሚገኝ ገዳም ገብተዋል። ይህ ቦታ ለአክሱም ቅርብ ሲሆን በዘመነ ሐዋርያት የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ በዓት ነበር። የሐዋርያው በትረ መስቀልም እስካሁን አለች።

ጻድቃነ ዴጌ ሕጋቸው አንዲት እርሷም ፍቅር ናት። ለዘመናት በፍቅረ ክርስቶስ ታሥረው ፍቅርን ለብሰው በፍቅር ኑረዋል። ሁሌም በሃያ ዘጠኝ የጌታችንን ስም እየጠሩ ጽዋ ጠጥተዋል። ስለ ፍቅራቸውም ጌታችን ሦስት ሺህ አንደኛ ሆኖ ነዳይ መስሎ አብሯቸው ጠጥቷል።
በመጨረሻም ሦስት ሺህው በአንድነት ተሠውረዋል።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እኛንም በወዳጆቹ ጸሎት ይማረን።

ጥር ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ጻድቃን ቅዱሳን ማኅበረ ዶጌ (ዴጌ ጻድቃን)
፪.አባ ገብረ ናዝራዊ ዘቃውንት (ኢትዮጵያዊ)
፫.ቅድስት አክሳኒ ፈላሲት
፬.ቅዱስ ሰርያኮስ ሰማዕት
፭.አባ እስጢፋኖስ ገዳማዊ
፮.ከድሮዋ ሮም የተነሱ ቅዱሳት አንስት
፯.ቅዱስ ታዴዎስ ዘጽላልሽና ቅዱስ ማትያስ (ሰማዕታት)
፰.አቡነ ገብረ መርዓዊ (ልደታቸው)

ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪.ቅድስት አርሴማ ሰማዕት
፫.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እናታችን
፬.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍፃሜተ ሰማዕት
፭.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፮.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)

"ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፱-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ቅዱስ ኄኖክ፣ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ እና ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ኄኖክ <3

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ቅዱስ ኄኖክ ከአዳም ሰባተኛ ትውልድ ነው። አዳም፣ ሴት፣ ሔኖስ፣ ቃይናን፣ መላልኤል፣ ያሬድ ብለን ሰባተኛው ኄኖክ ነውና።

ቅዱሱ የማቱሳላ አባትም ነው። አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉም ሞትን ያላየ ብሔረ ሕያዋን የገባ የመጀመሪያው ሰው ሁኗል። ለአዳም ልጆችም ተስፋ ድኅነት እንዳለ ማሳያ ሁኗል። "በአቤል አፍርሆሙ ወበኄኖክ አንቅሆሙ" እንዳለ ሊቁ።

ቅዱስ ኄኖክ በ፲፬፻፹፮ ዓ.ዓ የመጀመሪያውን የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል (መጽሐፈ ኄኖክን) ከመጻፉ ባሻገር በብዙ ሥፍራ በክብር ተጠቅሶ ይገኛል።

<3 ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ <3

ይህ ቅዱስ ሐዋርያ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን መብራት ነው። ወደ ክርስትና የመጣው በ፵ዎቹ ዓ.ም አካባቢ ሲሆን አሳምኖ ለቅድስና ያበቃው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው።

በጊዜውም በነበረው ትጋትና ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል። ሆዱንም እጅግ ያመው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ሲጠራው "የምወድህ ልጄ" እያለ ነበር። በኤፌሶንም ጵጵስናን ሹሞ ሁለት መልእክታትን ልኮለታል። ቅዱስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት አገልግሎ በሰማዕትነት ዐርፏል።
ዛሬ ሥጋው ከኤፌሶን ወደ ቁስጥንጥንያ የፈለሰበት ነው። ጊዜውም ፫፻፴ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ ላይ እንደሆነ ይታመናል።

<3 ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት <3

ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም። የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው።

በሦስቱ ሰማያት ካሉት ዘጠኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው። መልአኩ እጅግ ርኅሩኅ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው። ለኖኅ መርከብን ያሳራው ከጥፋት ውኃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው።

በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው። ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እስራልዩ" ይባላል። "የእስራኤል ረዳት" እንደ ማለት ነው። ዛሬ ደግሞ የሊቀ መልአኩ ቅዳሴ ቤቱ ነው።

የቅዱሳኑ በረከት ይደርብን።
የይቅርታ ጌታ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አይተወን፤ አይጣለንም።

ጥር ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኄኖክ ነቢይ (ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረገበት)
፪.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
፫.ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት (ከሰባቱ ሊቃናት አንዱ)
፬.ቅዱስ አባ ቢፋሞን ሰማዕት
፭.ቅዱስ ሰራብዮን ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ
፪.አቡነ መብዓ ጽዮን
፫.አባ መቃርስ ርዕሰ መነኮሳት
፬.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፭.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
፮.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ

"የተጠራችሁለት ለዚህ ነው። ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም። ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም። ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራንም ሲቀበል አልዛተም።
.....እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።"
(፩ጴጥ ፪፥፳፩-፳፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥር ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕተ ሮሜ
፪.ቅዱሳን ባስልዮስና ጎርጎርዮስ
፫.ብፁዕ አባ ጴጥሮስ ጽሙድ (ለምጽዋት ራሱን የሸጠ አባት)
፬.ቅዱስ ሰብስትያኖስ ሰማዕት
፭.ቅዱስ አስኪላ ሰማዕት
፮.አቡነ ሕፃን ሞዐ (ልደታቸው)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፪.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፫.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፬.አቡነ አቢብ
፭.አባ አቡፋና

"የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ። ተፈተኑ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ፣ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ፣ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና።"
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ <3

<3 ልደት <3
መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው። እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ፣ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል።

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል። በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል።

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ ቀን በ፲፪፻፮ ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን በ፲፪፻፯ ዓ/ም ነው። በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል። ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል።

<3 ዕድገት <3
የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል። ይህንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል። በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት፣ ሐዲሳትን) ተምረዋል። በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል። ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል።

<3 መጠራት <3
አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ።

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ። "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን። ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ። ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በግርማ ዐረገ። ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም። ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ።

<3 አገልግሎት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ። በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ሁለት መልክ ነበራት።
፩ኛ.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል።
፪ኛው. ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር።

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ። ሕዝቡንና መሳፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል።

<3 ገዳማዊ ሕይወት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል። እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በሦስት ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል።

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለአሥራ ሁለት ዓመታት፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለሰባት ዓመታት፣ በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለሰባት ዓመታት በአጠቃላይ ለሃያ ስድስት ዓመታት አገልግለዋል።

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለሃያ ሁለት ዓመታት ቆመው ጸልየዋል። በተሰበረ እግራቸውም ስድስት ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለሰባት ዓመታት ጸልየዋል።

<3 ስድስት ክንፍ <3
ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል። ጻድቁ ምድረ እስራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ፣ እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር።

ከወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው። ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር።

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም። በገሃድ፦
በቤተ መቅደስ ብስራቱን፣
በቤተ ልሔም ልደቱን፣
በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣
በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣
በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር።

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ።
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አባታችንን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው።
በዚያም፦
የብርሃን ዓይን ተቀብለው፣
ስድስት ክንፍ አብቅለው፣
የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣
ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣
ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው፣
ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል።

<3 ተአምራት <3
የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው።
ሙት አንስተዋል፣
ድውያንን ፈውሰዋል፣
አጋንንትን አሳደዋል፣
እሳትን ጨብጠዋል፣
በክንፍ በረዋል፣
ደመናን ዙፋን አድርገዋል።

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል። በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል። በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና።

<3 ዕረፍት <3
ጻድቅ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው፣ መከራን በብዙ ተቀብለው፣ እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ ቀን በ፲፫፻፮ ዓ/ም ዐርፈዋል። ጌታ፣ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል። አሥር ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል።

በዚህች ዕለት አባታችን ተክለ ሃይማኖት ለሃያ ሁለት ዓመታት የቆሙበት ቀኝ እግራቸው መሠበሩንና በአንድ እግራቸው ለሰባት ዓመታት ቆመው መጸለያቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስባለች።

አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ ምልጃ ክብራቸውን ያድለን። በረከታቸውም በዝቶ ይደርብን።

ጥር ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
፪.ቅድስት ማርያ ግብጻዊት
፫.ታላቁ አባ ቢፋ
፬.አባ አብሳዲ ቀሲስ
፭.ቅዱሳን ጻድቃነ ሐውዚን
፮.እጨጌ መርሐ ክርስቶስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ ዘዮሐንስ (ዘክብራን ገብርኤል - ጣና)
፪.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ
፫.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ
፬.ቅዱስ ሙሴ ጸሊም
፭.ቅዱስ አጋቢጦስ
፮.ሃያ አራቱ ካህናተ ሠማይ

"በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሠር አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ።
.....በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።
የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።"
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

<3 አስቀድሞ ኃይለኛ ጠንቋይ የነበረውና በኋላም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተአምሩ አሳምኖ አስጠምቆ ለሰማዕትነት ያበቃው ቅዱስ አትናስዮስ <3

ንጉሥ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተ መንግሥቱ ገብቶ በከሃዲያኑ ሰባው ነገሥታት ፊት ክርስቲያን መሆኑን በመመስከር የጌታችንን አምላክነት መሰከረ። ዱድያኖስም የቅዱስ ጊዮርጊስን ማንነቱን ከተረዳ በኋላ ‹‹አንተማ የኛ ነህ። በዐሥር አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ?›› አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም ‹‹ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን። እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም።›› አለው። በዚህ ጊዜ ዱድያኖስ እጅግ ተናዶ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን አደረሰበት። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ጌታችንን ‹‹ይህን ከሃዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰዳት።›› በማለት መከራውን ይታገስ ዘንድ ለመነው። እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ፈቃዱን ይፈጽምለት ብዙ በመከራው ሁሉ ጽናትን ሰጥቶታል። ሦስት ጊዜም ከሞት አስነሥቶታል። ቅዱስ ጊዮርጊስም የደረሱበት እጅግ አሠቃቂ መከራዎች የሰው ኅሊና ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸው ናቸው። በመጀመሪያም ዱድያኖስ በእንጨት ላይ ካሰቀለው በኋላ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው። ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሒድ አለው። ጌታችንም ቅዱስ
ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል። ዳግመኛም በሰባ ችንካሮች አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ። ሥጋውንም በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነሰነሰበት። ሥጋውም ተቆራርጦ መሬት ላይ ወደቀ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ ከፈወሰውና ‹‹ገና ስድስት ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ። ሦስት ጊዜ ትሞታለህ፤ በአራተኛውም ታርፋለህ።›› ካለው በኋላ በመከራውም ሁሉ እርሱ እንደማይለየው ነገረው።

ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚያ ካደረሰበት አሠቃቂ መከራዎች ሁሉ ድኖ ፍጹም ጤነኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ እጅግ ደንግጦ ‹‹የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ብዙ ወርቅ እሰጠዋለሁ።›› ብሎ ተናገረ። አትናስዮስ የተባለ መሠርይ አንዲትን ላም በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ስትሞት ለንጉሡ አሳየውና ቅዱስ ጊዮርጊስን እንደሚያሸንፍ ምልክት አሳየ። ንጉሡም ‹‹ያሸንፍልኛል›› ብሎ ደስ አለው። መሠርይውም ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞበት እንዲጠጣው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል። በዚህም ጊዜ ጠንቋዩ እጅግ ተገርሞ ‹‹ማረኝ›› ብሎ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግሩ ሥር ወደቀ። ዳግመኛም ‹‹አምላክህ አምላኬ ይሁነኝ።›› ብሎ ለመነው። ሰማዕቱም የዚያን መሠርይ ጠንቋይ መመለሱንና ማመኑን አይቶ የቆመባትን መሬት በእግሩ ረግጦ ውኃን አፍልቆ ወደ ጌታችን በጸሎት ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስ በመንፈስ መጣና መሠርይ የነበረውን ሰው አትናስዮስን አጠመቀው። አትናስዮስም ‹‹ከቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም።›› በማለት የጌታችንን አምላክነት በከሃድያኑ ነገሥታት ፊት መስክሮ በዛሬዋ ዕለት አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ በሰማዕትነት ዐርፏል።

የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስና በተአምሩ አሳምኖ አስጠምቆ ለሰማዕትነት ያበቃው የቅዱስ አትናስዮስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን። በጸሎታቸውም ይማረን!

(ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ዑራኤል <3

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል፦
፪.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጓታል። በሠረገላ ብርሃን ጭኖ በክንፎቹም ተሸክሞ አስቅድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል። በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ፣ የምትለምንና የምትማልድ ሆናለች። ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች።
፪.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መርቶ አምጥቷታል። በክንፉ ተሸክሞ በአራት አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጓል።
፫.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ አፍስሷል።
፬.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል።

አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን ይፈጽምልን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ጥር ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ እንጦንስ (የመነኮሳት አባት - የበርሐው ኮከብ ልደቱና ዕረፍቱ)
፪.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላዕክት (ለተጠሙ ጽዋዓ ልቡናን የሚያጠጣ ምሥጢር ገላጭ መልአክ)
፫.ቅዱስ ሚናስ ኤጲስ ቆጶስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፪.ቅዱስ ደቅስዮስ ኤጲስ ቆጶስ
፫.አባ ጳውሊ የዋህ

"እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ። መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል። ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።"
(ማቴ ፲፮፥፳፬-፳፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና (ለማርያም)
ወረደ ወልድ እምዲበ ልዕልና
ጠሊሳነ ንግሥ ሶቤሃ ከደና።"

(በማርያም ዕረፍት ጊዜ ወልድ ከልዕልና ወረደ፤ የንግሥና (የክብር) መጐናጸፊያን በዚያን ጊዜ ሸፈናት።)
(ቅዱስ ያሬድ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሊቅ <3

ለዚህ ቅዱስ አባት ብፁዕ መባል ተገብቷል። ክቡር፣ ምስጉን፣ ንዑድ ሰው ነውና። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቂሣርያ ቀጰዶቅያ የተወለደው ቅዱሱ ሰው ለደሴተ ኑሲስ ብርሃኗ ነው። አባቱ ኤስድሮስ፣ እናቱ ኤሚሊያ፣ ወንድሞቹ ቅዱሳን "ባስልዮስ፣ ጴጥሮስ፣ መክርዮስና መካርዮስ" ይባላሉ።

የተቀደሰች እኅቱም ማቅሪና ትባላለች። ከዚህ የተባረከ ቤተሰብ ለቅድስና ያልበቃ አንድም ሰው የለም። ሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከማር በጣፈጠ ዜና ሕይወቱ እንደ ተጻፈው፦
በልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል።
ሥጋውያን ጠቢባንን ያሳፍር ዘንድም የግሪክን ፍልሥፍና በልኩ ተምሯል።
በታላቅ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ መሪነት ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል።
በመንኖ ጥሪት ተመስግኗል።
ተገብቶትም በኑሲስ ደሴት ላይ ጳጳስ ሆኗል።
እርሱ ሲሔድ በከተማው የነበሩ ክርስቲያኖች አሥራ አንድ ብቻ የነበሩ ሲሆን እርሱ ሲያርፍ ክርስቶስን የማያመልኩ ሰዎች ቁጥር አሥራ አንድ ብቻ ነበር።
ቅዱስ ጐርጐርዮስ ፍጹም ሊቅ ነበርና ከቁጥር የበዙ ድርሳናትን ደርሷል።
ታላቁን ጉባኤ ቁስጥንጥንያን (በ፫፻፹፩ ዓ.ም) መርቷል። ብዙ መናፍቃንንም አሳፍሯል።

ከንጽሕናው የተነሳ መላእክት ያቅፉት እመ ብርሃንም ትገለጥለት ነበር። ለሠላሳ ሦስት ዓመታት እንደ ሐዋርያት ኑሮ በዚህ ቀን ድንግል ጠራችው። ቀድሶ አቁርቦ ሕዝቡን አሰናብቶ የቤተ መቅደሱን ምሰሶ እንደ ተደገፈ ዐርፎ ተገኝቷል። በዝማሬና በፍቅር ቀብረውታል።

<3 ቅድስት ኢላርያ <3

"ኢላርያ" ማለት "ፍሥሕት (ደስ የተሰኘች)" እንደ ማለት ነው። ከተባረኩ ቅዱሳት አንስት ትልቁን ሥፍራ ትይዛለች። ማን እንደ እርሷ!

ቅድስት ኢላርያ ማለት፦
የታላቁ ንጉሠ ነገሠት የደጉ ዘይኑን (Emperor Zenon) የበኩር ልጅ፣
በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተወለደች፣
ትምሕርተ ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተማረች፣
ምድራዊ ንግሥናን ንቃ ፍቅረ ክርስቶስን የመረጠች፣
የአባቷን ቤተ መንግሥት ትታ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ (ገዳመ አስቄጥስ) የወረደች፣
ስሟን ከኢላርያ ወደ ኢላርዮን ቀይራ በወንዶች ገዳም የመነኮሰች፣
ራሷን በፍጹም ገድል ቀጥቅጣ ከወንዶቹ በላይ በሞገስ ከፍ ከፍ ያለች፣
ትንሽ እኅቷን ጨምሮ በርካቶችን የፈወሰች፣
በእርሷ ምክንያት ለግብጽና በመላው ዓለም ለሚገኙ ገዳማት ብዙ ቸርነት በዘይኑን የተደረገላት ታላቅ እናት ናት።

ቅድስት ኢላርያ ማንም ሴት መሆኗን ሳያውቅባት አባ ኢላርዮን እንደ ተባለች በዚህች ቀን ዐርፋለች። ቤተ ክርስቲያንም ቅድስቲቱንና የተባረከ አባቷን ዘይኑንን ስለ በጐነታቸውና ውለታቸው ታስባቸዋለች።

የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ፣ ፍቅሯ፣ ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን።

ጥር ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.በዓለ አስተርዕዮ ማርያም (እመቤታችን ከዕረፍቷ በኋላ ለደቀ መዛሙርት በዚሁ ቀን ተገልጣ ነበር።)
፪.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ (ታላቅ ሊቅና ጻድቅ)
፫.ቅድስት ኢላርያ እናታችን (የዘይኑን ንጉሥ ልጅ)
፬.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
፮.ቅዱስ ኒቆላዎስ ሰማዕት
፯.አባ ፊቅጦር
፰.አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግሉ
፱.አቡነ ተስፋ ኢየሱስ ዘጎጃም
፲.አቡነ ኤልያስ ዘመርጡ ለማርያም
፲፩.ቅድስት ማርያም ክብራ ዘደብረ ጽላልሽ
፲፪.ቅዱሳን ጳውሎስና ቀሲስ ሲላስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ ምዕመነ ድንግል
፪.አባ አምደ ሥላሴ
፫.አባ አሮን ሶርያዊ
፬.አባ መርትያኖስ
፭.አበው ጎርጎርዮሳት

"ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን። እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን።
አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ። አንተና የመቅደስህ ታቦት።
ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ። ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው።"
(መዝ ፻፴፩፥፯-፱)

"ወዳጄ ሆይ! ተነሺ። ውበቴ ሆይ! ነዪ።
በዓለት በንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ!ቃልሽ መልካም ውበትሽም ያማረ ነውና መልክሽን አሳዪኝ። ድምጽሽንም አሰሚኝ።"
(መኃ ፪፥፲፫-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…
Subscribe to a channel