እንኳን ለጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አቡነ ገብረ ሕይወት <3
ጻድቁ የተወለዱት ግብጽ (ንሒሳ አካባቢ) ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ፣ የቅዱሳን የበላይ፣ ተጋድሎአቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው።
የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አንደበት ይኖራል?
እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል?
ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን?
አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ
እህል ያልቀመሱ ምግባቸው ምስጋና ነውና።
ልብስ ያልለበሱ ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና።
ሐዋርያዊ ሆነው ከግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት ሲሆኑ ሃገራችንን አስምረው አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ ዐርፈዋል።
ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ገብረ ሕይወትም ይባላሉ። በአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ወንጌልን ሰብከዋል። በዚህም በሚሊየን (አእላፍ) ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል።
ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል። እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል። ለየት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው። ከእልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና።
የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለመቶ ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው።
ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት። በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ነው። ፍጥረታትን ሁሉ አዝዘው መጋቢት ፭ ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል።
ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ።
"ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ
ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ
ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ
ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ
ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ።" እንዲል።
የጻድቁ በዓል ጥቅምት ፭ ቀን የሚከበረው ብዙ ጊዜ መጋቢት ፭ ቀን ዐቢይ ጾም ውስጥ ስለሚውል ተውላጥ (ቅያሪ) ሆኖ ነው።
ቸር አምላክ ከጻድቁ ዋጋና በረከት ይክፈለን።
መጋቢት ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ (አባ ገብረ ሕይወት)
፪.ቅዱስ አባ ሰረባሞን (በምድረ ግብጽ ምንኩስናን ካስፋፉ ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ)
፫.አባ ግርማኖስ ጻድቅ (ሶርያዊ)
፬.ቅድስት አውዶክስያ ሰማዕት (ከከፋ የኃጢአት ሕይወት ተመልሳ ለቅድስና የበቃች እናት)
፭.ቅዱሳን ስምዖንና ሚስቱ አቅሌስያ (የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወላጆች)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፬.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
"ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል። ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም።"
(ማቴ ፲፥፵፩-፵፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ቆዝሞስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቆዝሞስ ሊቀ ጳጳሳት <3
"ጳጳስ" ማለት "አባት - መሪ - እረኛ" ማለት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ሥልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ ሦስት ናቸው። እነርሱም ዲቁና፣ ቅስና፣ ጵጵስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ ዘጠኝ ያህል ክፍሎች አላቸው። ከእነዚህም ከፍተኛው ሥልጣን ጵጵስና ነው።
ጵጵስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው። ሥልጣኑ በምድር "ሸክም፣ ዕዳ" ሲሆን በሰማይ ግን "ክብር" ነው። ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ጵጵስናን አይመኝም።
ቅዱስ ጳውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ጵጵስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ።" (፩ጢሞ. ፫፥፩) ማለቱን ይዞ "ሹሙኝ" ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው። ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል። የከፋው ግን የጳጳሱ ነው።
አንድ ጳጳስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም። ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና። ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው።" (ዮሐ. ፲፥፲፩) ስለዚህም ክህነት ( ጵጵስና) ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው።
አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የጵጵስና መንበሮችን መሥርተው ትምህርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል። ከእነዚህ መንበረ ጵጵስናዎች አራቱ የበላይ ናቸው።
እነዚህም፦
የቅዱስ ጴጥሮሱ የሮም፣
የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ፣
የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ጳውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው።
እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ ፬፻፵፫ (፬፻፶፩) ዓ.ም ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል። ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው።
የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ጳጳሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች፤ ታከብራለች።
በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን። እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና። ከእነዚህም መካከል አንዱ ቅዱስ ቆዝሞስ የእስክንድርያ (የግብጽ) ሃምሳ ስምንተኛ ሊቀ ጳጳሳት የነበረ አባት ነው። ዘመኑ እስልምና የሰለጠነበት ነበርና በዚያ ጊዜ እረኝነት (ጵጵስና) መመረጥ እንደ ዛሬው ዘመን ሠርግና ምላሽ አልነበረም። በከሃዲዎች እሳትና ስለት መከራን ለመቀበል መወሰን እንጂ።
ከስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ በዓለማችን ከተነሱ ሊቃነ ጳጳሳት ለግብጻውያኑ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ቦታ አላት። ምክንያቱም በወቅቱ በጎቻቸውን (ምዕመናንን) ለመጠበቅ ከግብጽ ከሊፋዎች የግፍ ጽዋዕን ጠጥተዋልና። ከእነዚህም አንዱ የእመቤታችን ፍቅር የበዛለትና በዚህ ቀን ያረፈው ቅዱስ ቆዝሞስ ነው።
አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን።
መጋቢት ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ቆዝሞስ (የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት)
፪.አባ በርፎንዮስ ክቡር
ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
፬.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭.አቡነ ዜና ማርቆስ
፮.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
"ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ። ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ። እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና። በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ።"
(ሮሜ ፲፮፥፲፯-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ከተባረከ ወር መጋቢትና ከሁለተኛው መንፈቀ ዘመን የመጀመሪያ ዕለት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
ወርኀ መጋቢት መዐልቱና ሌሊቱ እኩል አሥራ ሁለት ሰዓት ናቸው። ከዛሬዋ ዕለት ጀምሮ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት (መቶ ሰማንያ አምስት ቀናት) ከማይጠቅም ወሬ ተቆጥበን ከክፋትም ርቀን መልካሙን የእግዚአብሔር ጐዳና ለመከተል ራሳችንን ልናዘጋጅ ይገባል።
በዚህች ዕለትም ከአዳም ስምንተኛ ትውልድ የሆነው አባታችን ማቱሳላ በዓለ ዕረፍቱ ይከበራል። ቅዱስ ማቱሳላ የጻድቅ ሰው ኄኖክ ልጅ የደጉ ላሜሕ አባት ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ረዥም ዕድሜ (ዘጠኝ መቶ ስልሳ ዘጠኝ ዓመት) የቆየ ባለ ረዥም ዕድሜ አባት ነው። ከአሥሩ ቅዱሳን አባቶች አንዱ ነው።
አሥሩ ቅዱሳን አባቶች ማለት፦
ቅዱስ አዳም አባታችን፣
ሴት፣
ሔኖስ፣
ቃይናን፣
መላልኤል፣
ያሬድ፣
ኄኖክ፣
ማቱሳላ፣
ላሜሕና
ኖኅ ናቸው።
ዕድሜ ማቱሳላን ለንስሐ አምላከ ቅዱሳን ይስጠን!
መጋቢት ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ማቱሳላ
፪.ቅዱስ በርኪሶስ ዘኢየሩሳሌም
፫.ቅዱስ እለእስክንድሮስ
፬.ቅዱስ መርቆሬዎስ
፭.አባ ሚካኤል ዘሃገረ አትሪብና አባ ዮሐንስ ዘሃገረ ቡርልስ (ሃይማኖተ አበውን፣ ግጻዌንና ስንክሳርን ያዘጋጁ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፬.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፭.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
"ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ። ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቧልና። ሌሊቱ አልፏል ቀኑም ቀርቧል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ።"
(ሮሜ ፲፫፥፲፩-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለኢትዮጵያዊቷ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 እመ ምዑዝ (እም ምዑዝ) <3
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሐዋርያዊት፣ ጻድቅትና ሰማዕት ናት።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፦
ደቡብ ጐንደር አካባቢ ከነበሩ ወላጆቿ ተወልዳ በመንፈሳዊ ማደግ አድጋ ዘርዐ ክርስቶስ ለተባለ ደግ ሰው አጋቧት። ከሥርዓተ ተክሊል በኋላ ሁለቱ ተስማምተው ለአርባ ዓመታት ባንድ ቤት እየኖሩ ድንግልናቸውን ጠብቀዋል። ቀን ቀን እንግዳ ሲቀበሉ ነዳያንን ሲያበሉ ይውላሉ። ሌሊት ደግሞ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ ያድሩ ነበር።
ከዓመታት በኋላ በብሥራተ መልአክ ቅዱስ ልጅ ወልደው በሰባት ዓመቱ ቅዱስ መልአክ ነጥቆ አሳርጎታል።
በዘመኑ አፄ ሱስንዮስ ሃይማኖታቸውን ሲክዱ ቅዱሳኑ ፍቅርተ ክርስቶስና ዘርዐ ክርስቶስ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። ከቆይታ በኋላ እናታችን በፈጣሪዋ ኃይል ከሞት ተነስታ ከኢትዮጵያ እስከ ኢየሩሳሌም በሐዋርያዊ አገልግሎት በርካቶችን አሳምና ታሪከኛ የሆነ ቤተ ክርስቲያን አንፃ በዚህ ዕለት አርፋለች።
ከቅድስት እናታችን በረከት አምላክ አይለየን።
የካቲት ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊት
፪.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
፫.ቅዱሱ ሕፃን (የፍቅርተ ክርስቶስ ልጅ)
፬.ቅዱስ ቢላካርዮስ ዘሃገረ አርሞኒ (አረጋዊ፣ ደራሲ፣ ጻድቅና ሰማዕት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪.ቅድስት አርሴማ ድንግል
፫.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
"መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ። አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።
ውበት ሐሰት ነው። ደም ግባትም ከንቱ ነው።
እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። ከእጇ ፍሬ ስጧት። ሥራዎቿም በሸንጐ ያመስግኗት።"
(ምሳሌ ፴፩፥፳፱-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ሊቅና ጻድቅ ቅዱስ አንስጣስዮስ እና አቡነ ዓምደ ሥላሴ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ አንስጣስዮስ ሊቅ <3
ቅዱስ አንስጣስዮስ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳ ሶርያዊ የነገረ መለኮት ሊቅ፣ ገዳማዊ ጻድቅና የመንበረ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ነበር። ቅዱሱ ርጉም አርዮስን ካወገዙ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት አንዱ ነው። በወቅቱ ታላላቅ ሊቃነ ጳጳሳት ሱባኤውንና ጉባኤውን የመሩ ሲሆን አንዱ ይህ ቅዱስ ነው።
ከአምስት ዓመታት በኋላም ብዙ ድርሳናትን ጽፎ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ በ፫፻፴ ዓ.ም አርፏል። ያረፈው ግን አርዮሳውያን ባቀረቡት ክስ በሃሰት ተመስክሮበት በግፍ ተሰዶ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለ ውለታው የውዳሴ ድርሳን ጽፎለታል።
<3 አቡነ ዓምደ ሥላሴ <3
እኒህ ታላቅ ጻድቅ ሐዋርያዊ አባት አቡነ ዓምደ ሥላሴ የትውልድ ሃገራቸው ጎጃም ሲሆን የተወለዱት በዚሁ ዕለት (የካቲት ፳፯) ነው። ጻድቁ በአፄ ሱስንዮስ ጊዜ በአሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ድንቅ ሠሪ፣ ተአምረኛና ገዳማዊ አባት ናቸው።
የካቲት ፲፮ ቀን መንኩሰው ወደ ተጋድሎ ገብተዋል። በዋልድባ በነበራቸው ቆይታም እመቤታችን ኪዳነ ምሕረት የካቲት ፲፮ ቀን እንድትከበር ማድረጋቸውም ይነገራል። ጻድቁ በሌሎች ገዳማትም የነበሩ ሲሆን ዛሬም ድረስ ረድኤታቸው የሚደረግበት ስማቸው የሚጠራበት ገዳም ግን ማኅበረ ሥላሴ ይባላል።
ገዳሙ የሚገኘው በሃገራችን ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በመተማ በርሃ ውስጥ ነው። ይህንን ቅዱስ ገዳም የመሠረቱትም ራሳቸው አባ ዓምደ ሥላሴ ናቸው። ገዳሙ ዛሬም ብዙ ምሑራንና መናንያን ያሉበት በደህና ሁኔታም የሚገኝ ነው። ግን በርሃውን የኔ ብጤ ደካማ ሰው የሚችለው አይደለም።
ስለ ጻድቁ ዓምደ ሥላሴ ከሚነገሩ ታሪኮች ቅድሚያውን የሚይዘው የተዋሕዶ ጠበቃነታቸው ነው። በ፲፮፻፫ ዓ.ም ጴጥሮስ (ፔድሮ) ፓኤዝ የሚባል ካቶሊካዊ እሾህ ወደ ሃገራችን ገብቶ ነበርና ንጉሡን ሱስንዮስን አባብሎ ተዋሕዶን አስካዳቸው። ነገሩ ውስጥ ለውስጥ ሲበስል ቆይቶ በ፲፮፻፱ ዓ.ም በመገለጡ እነ ራስ ዮልዮስ ለሃይማኖታቸው ጠዳ ላይ ተዋግተው ግንቦት ፮ ቀን ተሰው።
ይህ ነገር ሲሰማ ወንድ ሴት፣ ትልቅ ትንሽ ሳይመረጥ በገጠሩም፣ በከተማውም፣ በገዳሙም ያሉት ሁሉ የተዋሕዶ ልጆች መንቀሳቀስ ጀመሩ። ሰባት ዓመታት እንዲህ አልፈው በ፲፮፻፲፮ ዓ.ም ግጭቱ በይፋ ተጀመረ።
"ተዋሕዶን ካልካዳችሁ" በሚል በቀን እስከ ስምንት ሺህ ሰው በሰይፍ ታረደ። ይህን ያደረጉት ደግሞ አልፎንሱ ሜንዴዝ፣ ንጉሡ ሱስንዮስና ጀሌዎቻቸው ነበሩ።
በጊዜውም ከቤተ መንግሥት እነ ንግሥት ወልድ ሰዓላ (የሱስንዮስ ሚስት)፣ ከጻድቃን አበው ዘርዓ ቡሩክ ዘግሺ፣ ሐራ ድንግል ዘደራ፣ ምዕመነ ድንግል ዘጩጊ፣ ዓምደ ሥላሴ ዘማኅበረ ሥላሴ፣..... ከቅዱሳት እነ ፍቅርተ ክርስቶስ፣ ወለተ ጴጥሮስ፣ ወለተ ጳውሎስ፣ እኅተ ጴጥሮስ፣..... ለሃይማኖታቸው ተዋሕዶ ጥብቅና ቆመው ሕዝቡን አስተማሩ፤ መከራም ተቀበሉ።
ብዙ ኢትዮጵያውያን የመከራ ጽዋን ተጐንጭተው ለክብር ከበቁ በኋላ የእግዚአብሔር ፍርድ ተገለጠ። በጻድቃኑ እነ አባ ዓምደ ሥላሴ ሐዘን ንጉሡ ታመመ። ምላሱ ተጐልጉሎ ወጣ።
በዚህ ጊዜ አቤቶ ፋሲለደስ ለአባ ዓምደ ሥላሴና ለሌሎቹ ቅዱሳን "አባቴን አድኑልኝ! ተዋሕዶም ትመለስ።" አላቸው። ጻድቁም ከባልንጀሮቻቸው ጋር ጸልየው ንጉሡን አዳኑት። በፈንታውም ይህንን አሳወጁ።
"ፋሲል ይንገሥ!
ሃይማኖት (ተዋሕዶ) ይመለስ!
የሮም ሃይማኖት ይፍለስ!"
ከዚህ በኋላ በ፲፮፻፳፬ ዓ.ም ፋሲል ሲነግሥ አባ ዓምደ ሥላሴ ለገዳማቸው ብዙ ቦታ አስከልለው በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል።
አምላከ ቅዱሳን በቀናችው እምነት ተዋሕዶ ሁላችንንም እስከ ፍጻሜ ዘመናችን ያጽናን። ከበረከተ ቅዱሳንም ይክፈለን።
የካቲት ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ አንስጣስዮስ ርቱዓ ሃይማኖት (ዘአንጾኪያ)
፪.አቡነ ዓምደ ሥላሴ
ወርኀዊ በዓላት
፩.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪.አቡነ መብዐ ጽዮን ጻድቅ
፫.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፬.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
፭.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፮.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፯.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
"የተጠራችሁለት ለዚህ ነው። ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም። ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም። ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራንም ሲቀበል አልዛተም።.....
እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።"
(፩ጴጥ ፪፥፳፩-፳፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ አቡፋና እና ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አባ አቡፋና <3
ታላቁ አባ አቡፋና፦
በምድረ ግብጽ ተጋድሏቸውን የፈፀሙ፣
በመዐልት አምስት መቶ ጊዜ በሌሊትም አምስት ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ይጸልዩ የነበሩ፣
በአርባ ቀን አንድ ጊዜ ብቻ እህል ይቀምሱ የነበሩና ሙሉ ዘመናቸውን በበርሃ በታላቅ ጽሙና የፈፀሙ አባት ናቸው።
ጻድቁ በጣም የሚታወቁት ከማበጡ የተነሳ እጅግ ግዙፍ በነበረ እግራቸው ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስለ መድኃኔ ዓለም ፍቅር አልቀመጥም፤ አልተኛም ብለው ለአሥራ ስምንት ዓመታት በመቆማቸው ነው።
አሥራ ስምንት ዓመት የመቆማቸው ዜናስ እንደምን ነው ቢሉ፦
አንድ ቀን "እኔ ግን ከዚህ ዓለም የምለየው መቼ ይሆን?" ሲሉ አሰቡ። በእርግጥ ይህንን ሐሳብ ብዙ ሰዎች ሊያስቡት ይችላል። ሐሳቡ ጠቃሚም ያልተፈቀደም ነው።
፩. "ጠቃሚ ነው።" ያልኩት አንድ ሰው ሞት እንዳለ ካወቀ ወይም 'መቼ ነው የምሞተው' ብሎ ካሰበ ንስሐ ይገባል፤ ክፋትን ይተዋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ወገኔ ሁሉ እንደ አውሬ ሲባላ፣ ደም ሲያፈስ፣ ክፋትን ሲጐነጉን የሚውል "እሞት ባይ" ሳይሆን "እኖር ባይ" ሆኖ ነውና።
ግን ሞት በቅርቡ እንዳለ በኃያሉ አምላክ ፊት ራቁቱን ለፍርድ እንደሚቀርብ ለወገኔ ማን በነገረው!
፪. "ያልተፈቀደ ነው።" ያልኩት ደግሞ በሁለት ምክንያት ነው።
"ኢትበሉ ለጌሰም (ለነገ አትበሉ።)" የሚል አምላካዊ ቃል ስላለ።
ማቴ. ፮፥፴፬
ሰው (በተለይ ዓለማዊው) የሚሞትበትን ቀን ቢያውቅ አጭር ጊዜ ከሆነ ሽብር ጭንቀት ይበላዋል። ወዲህ ደግሞ ጊዜው ረዥም ቢሆን እንደ ሰብአ ትካት (ማለትም በኖኅ ዘመን እንደ ነበሩ ሰዎች) 'ብዙውን ልዝናናበት (ኃጢአት ልሥራበት')ና ንስሐ እገባለሁ።' ይላልና ነው።
በዚያውም ላይ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ቅዱስ ሰውና የነቢያት አለቃ ቅዱስ ሙሴ የሞቱን ጊዜ ጠይቆ እጅግ መቸገሩን መጥቀሱ በራሱ በቂ ነው። ጌታ "ዓርብ ቀን ትሞታለህ።" ብሎት ለሁለት ዓመታት ዓርብ ዓርብ ሲገነዝ ሲፈታ ኑሯል።
በመጨረሻም ዓርብ ቀን ድንገት መልአከ ሞት መጥቶበታል። ስለዚህ "ወድልዋኒክሙ ንበሩ - ተዘጋጅታችሁ ኑሩ። መባላችንን አስበን ልንኖር ግድ ይለናል።
ማቴ. ፳፬፥፵፬
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አቡፋና ይህንን የዕረፍታቸውን ነገር ሲያስቡ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ "ተርፈከ አሠርቱ ወሰመንቱ - አሥራ ስምንት ቀርቶሃል።" አላቸው። እርሳቸውም "ጌታዬ አሥራ ስምንት ምን?" ሲሉ ቢጠይቁትም ሳይመልስላቸው ተሠወረ።
ከደቂቃ እስከ ኢዮቤልዩ ብዙ አሥራ ስምንቶች አሉ። እርሳቸው ግን "አሥራ ስምንት ቀን ነው!" ብለው ለጌታ ተሳሉ። ስዕለታቸውም "ከዚህ በኋላ አልቀመጥም።" የሚል ነው። እየጾሙ እየጸለዩ ለአሥራ ስምንት ቀናት ቆሙ። ሞት አልመጣም።
"አሥራ ስምንት ሱባኤ ይሆን!" ብለው አሥራ ስምንት ሱባኤ (መቶ ሃያ ስድስት ቀናት) ቆመው ጸለዩ። አሁንም ሞት አልመጣም። "አይ! አሥራ ስምንት ወር ሊሆን ይችላል።" ብለው ለአሥራ ስምንት ወራት (ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር) ቆመው ተጉ። አሁንም ግን ሞት የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ።
ይህን ጊዜ ግን ወደ ፈጣሪ ለመኑ። "ጌታዬ! ያልከኝ ምን አሥራ ስምንት ነው?"
ቅዱስ መልአኩም መጥቶ "አቡፋና ሆይ! የቀረህ አሥራ ስምንት ዓመት ነውና ጽና።" ብሏቸው ተሰወረ። ልብ በሉልኝ "እስክሞት አልቀመጥም።" ብለው ተስለዋል።
ቅዱሱ ገዳማዊ በቃላቸው የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያን ነበሩና ለአሥራ ስምንት ዓመታት እንደተተከለ ምሰሶ ቆመው ጸለዩ፣ ጾሙ። እንዲህ ያሉትን ቅዱሳን ሊቃውንት፦
"ሰላም ለከ ጽኑዕ ከመ ዓምድ
ዘኢያንቀለቅሎ ሞገድ።"
(ማዕበለ ዓለም የማያናውጸው ብርቱ ምሰሶ ሆይ! ምስጋና ይገባሃል።) የሚሏቸው።
ስለ ቅዱሱ የተጻፈ አርኬም፦
"ሰላም ለቁመተ አቡፋና ዘአልቦ ኑታጌ
እስከ ተመሰለ እግሩ ከመ እግረ ነጌ።" ይላል። ከመቆም ብዛት አካላቸው ደቆ እግራቸው የዝሆን እግር እስኪመስል ወፍሮ ነበርና።
አባ አቡፋና በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን አርፈዋል።
<3 ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት <3
ቅዱስ እንጦኒ (Anthony) በትውልዱ ከሶርያ ዐረቦች ሲሆን በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን ያሳድድ፣ ካህናትን ይደበድብ፣ አብያተ ክርስቲያናትንም ያቃጥል ነበር። እግዚአብሔር በንስሐ ሲጠራው ግን ደግ፣ ጻድቅና ምርጥ ዕቃ ሆኖ ተገኘ። በመጨረሻም ከብዙ መከራ በኋላ ለሰማዕትነት በቅቷል።
አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ትጋት፣ ጽናት፣ ፍቅርና በረከት ያድለን። ከማስተዋልም አያጉድለን።
የካቲት ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
፪.ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት
፫.ቅዱሳን ሰማዕታት አውሳንዮስ፣ ፊልሞናና ሉቅያ ድንግል (የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ደቀ መዛሙርት)
፬.ቅዱስ ቶና ዲያቆንና ሰማዕት
፭.ቅዱስ ሚናስ ዘሃገረ ቁስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
"ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ። አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ። ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ።"
(፩ጢሞ ፩፥፲፪-፲፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
"አስተጋይድ ፈረሰከ ወአብድር እምዐውሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ለከ ይብለከ ልሣነ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት"
(ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዓውሎ ነፋስ ይልቅ ፈረስህን አቀዳድም ይልሃል የንጉሠ ነገሥት ምኒልክ አንደበት።)
እንኳን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ልመናው ጸሎቱ በረከቱ አማላጅነቱ በዕውነት ለዘለዓለሙ ይደረግልንና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው ተአምር ይህ ነው።
በዚያን ወራት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ አራት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በነገሡ በሃያ ስድስት ዓመት የምኒልክ የጦር አለቃ ገበየሁ ድል ከአደረጋቸው በኋላ እንደገና ምኒልክን ወግተው ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ሊገዙ የሮም ሰዎች መጡ።
ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ሀገሬ ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ ባስቸኳይ ይነሣ መስቀለ ሞቱንም ተሸክሞ ይከተለኝ እግዚአብሔር የወሰነልንን የባሕር ወሰን አልፎ ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት መጥቷልና ሲሉ ዓዋጅ አስነገሩ።
ዳግመኛም በፈረሶቻቸው መጣብር ላይ በጦራቸው አንደበት ላይ በጋሻቸው እምብርት ላይ የመስቀል ምልክት እንዲያደርጉ ጭፍሮቹን አዘዟቸው መስቀል ጠላትን ድል አድራጊ እንደሆነ አስቀድሞ ያውቁ ነበርና። ከዚያም ተነሥተው ወደ ትግራይ ክፍለ ሀገር ዘመቱና ከትግራይ አውራጃዎች አንዷ የምትሆን አድዋ ከምትባል አገር ደረሱ።
የሣህለ ማርያም ዳግማዊ ምኒልክ ሚስት ወለተ ሚካኤል እቴጌ ጣይቱም በንጉሡ ትዕዛዝ ታቦተ ጊዮርጊስን አስይዘው ከሊቀ ጳጳሱ ከአባ ማቴዎስ እንዲሁም ከቀሳውስቱና ከመነኮሳቱ ጭምር ከንጉሡ ጋር ወደ ጦርነቱ ተጓዙ።
በዚህም ጊዜ የአክሱም ጽዮን መነኮሳትና ካህናት የእመቤታችንን ሥዕል ይዘው ወደ ንጉሡ ወደ ምኒልክ መጥተው ከሊቀ ጳጳሱ ከአቡነ ማቴዎስ ጋር ተቀላቀሉ ከዚያም ሌሊቱን ሙሉ ጸሎተ ምሕላ ሲያደርሱ አደሩ።
ቅዳሜ ሌሊት ለእሑድ አጥቢያ የካቲት ፳፪ ንጉሡ ሣህለ ማርያም ምኒልክ የጦር ልብሳቸውን ለብሰው ከሠራዊታቸው ጋር ወደ ጦር ግንባር ሄዱ። ከዚያም ከሮማውያን የጠላት ጦር ጋር ተገናኝተው ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጦርነቱን ጀመሩ። የንጉሡ የሣህለ ማርያም ምኒልክ ሚስት ወለተ ሚካኤል እቴጌ ጣይቱም ሌሊት በታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስና በእመቤታችን ሥዕል ፊት በጸሎትና በስግደት አድረው ሲነጋ ወደ ጦርነቱ ቦታ በመሔድ እጅግ በሚያስደንቅ አነጋገራቸው ኃይለ ቃል በጦርነቱ መካከል እየተገኙ ለንጉሡ ወታደሮች የሞራልና የብርታት ድጋፍ ይሰጡ ነበር። በዕውነትም ለተመለከታቸው ሁሉ እንደ ኃይለኛ ተጋዳይ አርበኛ ይመስሉ ነበር እንጂ የሴቶች የተፈጥሮ ባሕርይ በእርሳቸው ላይ አይታይባቸውም ነበር።
የንጉሡም ወታደሮች የንግሥቲቱን የጀግንነት አነጋገር በሰሙ ጊዜ በእሳት ላይ እንደተጣደ የብረት ምጣድ ልባቸው ጋለ፤ ይልቁንም ላም እንዳየ አንበሳና የፍየል መንጋ እንዳየ ነብር እየተወረወሩ በጦርነት መካከል በመግባት የጠላትን ጦር በሰይፍ ይጨፈጭፉት ነበር። መጽሐፍ ሹመቱን ሽልማቱን ያየ አርበኛ ከጦርነት ከሰልፍ ወደ ኋላ አያፈገፍግም ብሎ ተናግሯልና።
በዚያም ጊዜ ንጉሡ ሣህለ ማርያም ምኒልክ በጦርነቱ መካከል ሳሉ ሊቀ ጳጳሱ አባ ማቴዎስ እንዲሁም የአክሱም መነኮሳትና ሌሎቹ ካህናት በሙሉ ታቦተ ጊዮርጊስንና ሥዕለ ማርያምን ይዘው ከንጉሡ በስተኋላ በደጀንነት ቆመው ጸሎተ ምህላ ያደርሱ ነበር። ንግሥቲቱ ወለተ ሚካኤል እቴጌ ጣይቱም በጸሎት ጊዜ በመዓልትም በሌሊትም ከእነርሱ አልተለዩም ነበር።
የጽዮን አገልጋዮችም በእግዚአብሔር የሕጉ ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር።
በዚህም ዕለት ይኸውም የካቲት ፳፫ ቀን በሮማውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሆነ በዚህም ጊዜ በሰማይ ታላቅ ተአምር ተደረገ ማለትም የቀስተ ደመና ምልክት ታየ ከዚያም ከቀስተ ደመናው ውስጥ መልኩ አረንጓዴ የሚመስል ጢስ ይወጣ ነበር። ከዚህም ጢስ ውስጥ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ያለ ድምጽ ተሰማ።
ከዚህም የነጎድጓድ ድምፅ የተነሣ በሮማውያን ወታደሮች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ሽብር ሆነ ለመዋጋትም አልቻሉም፤ ይልቁንም ኃያሉ ገባሬ ተአምር ማር ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምባ ላይ ፈረስ ተቀምጦ ከነፋስ ሩጫ ይልቅ እየተፋጠነ በዓየር ላይ በተገለጸ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም እያሉ ወደቁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አምላካቸው ሊረዳቸው መጣ እንግዲህ ማን ያድነናል አሉ፤ ምድር ጠበበቻቸው በዚህም ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሮምን የጦር ሠራዊት ፈጁዋቸው። የተረፉትንም ማረኳቸው ፈጽመውም እስኪያጠፏቸው ድረስ በሮማውያን ላይ በእግዚአብሔር ሥልጣን የኢትዮጵያውያን እጅ እየበረታች ሄደች።
ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ሣህለ ማርያም ምኒልክ በእግዚአብሔር ኃይልና በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት የሮማውያንን የጦር ሠራዊት በጦርነት ድል አድርገው የድል አክሊል ተቀዳጁ።
ስለዚህም በዳዊት የምስጋና ቃል የድል ዘውድ ያቀዳጀኝን እግዚአብሔርን ባለ ዘመኔ አመሰግነዋለሁ፤ ለፈጣሪዬም እዘምራለሁ አለ ሕዝቡም ሁሉ በክብር ከፍ ከፍ ያለ እግዚአብሔርን በፍጹም ምስጋና እናመሰግነዋለን፤ የሮማውያንን ኃይል ቀጥቅጦ አጥፍቷልና ሠረገሎቻቸውንም ሠባብሯልና፤ ሠራዊቱንም ሁሉ በምድር ላይ በትኗልና እያሉ አመሰገኑ። በፈጣሪያቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል በጦርነቱ መካከል የረዳቸውን ቅዱስ ጊዮርጊስንም በፍጹም ማድነቅ አደነቁት።
የሮማም የጦር ሠራዊት በኢትዮጵያዊያን ፊት ተዋረዱ ዳግመኛም በኢትዮጵያ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። በምኒልክም ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ከጦርነት ለዓርባ ዓመት ያህል ዓረፈች።
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክም ከዓድዋ ጦርነት ከተመለሱ በኋላ አዲስ አበባ ከተማ መካከል በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተ ክርስቲያን አሠሩ። ስሟንም ገነተ ጽጌ ብለው ሰየሟት። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጦርነት ቦታ ሁሉ ይረዳቸው ነበርና።
<3 ልመናው ክብሩ በእኛ ለዘለዓለሙ በዕውነት ይደርብን!
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ይክፈለን። <3
(ምንጭ፦ ተአምረ ጊዮርጊስ)
(የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ ሰንበት ት/ቤት/St. George Church Sunday School)
የካቲት ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ቡላ
፪.ቅዱሳን ሰማዕታተ ፋርስ (ፍልሠታቸውና ቅዳሴ ቤታቸው)
፫.ቅዱስ አባ ማሩና ጻድቅ ኤጲስ ቆጶስ (የፋርስ ሰማዕታትን አጽም የሠበሠበ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፬.አባ እንጦንዮስ (አበ መነኮሳት)
፭.አባ ጳውሊ የዋህ
"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን።' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ ፰፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ አናሲሞስ ሐዋርያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ድንግል ማርያም <3
የአምላክ እናቱ እመ ብርሃን ድንግል ማርያም፦
በሦስት ወገን (በሥጋ፣ በነፍስ፣ በልቡና) ድንግል
በሦስት ወገን (ከኀልዮ፣ ከነቢብ፣ ከገቢር) ንጽሕት
ሳትጸንስ፣ በጸነሰች ጊዜና ከጸነሰች በኋላ ድንግል
ጌታን ሳትወልድ፣ በወለደችው ጊዜና ከወለደችው በኋላ ድንግል ስትሆን እናትም ድንግልም መሆኗን አምነን እንመሰክራለን።
እመቤታችን ከፍጥረት ሁሉ በላይ ክብርትና ንዕድ ናት። ሊቃውንት አበው እንዳስተማሩን በዚህ ዕለት እንዲህ ብለን እንጸልያለን።
"ረስዪ ፍና ትሕትና አእጋርየ ይሑሩ
ትዕቢትሰ ለአምላክ ጸሩ።"
(እመቤቴ ሆይ ትዕቢትን አምላክ ይጠላልና እግሮቻችን በትሕትና እንዲሔዱ አድርጊ።)
<3 ቅዱስ አናሲሞስ ሐዋርያ <3
በዘመነ ሐዋርያት ምስጉን ከነበሩ አበው አንዱ ቅዱስ አናሲሞስ ነው። ስለ ቀና አገልግሎቱና መልካም እረኛነቱ አባቶቻችን ሐዋርያት አብዝተው በቀኖናቸው መስክረውለታል። እርሱ ከኃጢአት ኑሮ ወደ ዘላለማዊ የቅድስና ሕይወት መጥቷልና።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በሮም ከተማ የሚኖር ፊልሞና የሚባል አንድ ባለጸጋ ነበር። ይህ ሰው በስብከተ ቅዱስ ጳውሎስ አምኖ ክርስቲያን ሆነና በመንፈሳዊ አገልግሎት ተጠመደ። ነገር ግን ከአገልጋዮቹ መካከል ያላመነ አንድ ሰው ነበር። "ተጽዕኖ አላደርግበትም።" ብሎ ዝም ይለዋል። ግን ክርስትና እንዲገባው ለተልዕኮ መንፈሳዊ በሚሔድበት ሥፍራ ያስከትለው ነበር።
አገልጋዩ ግን በመለወጥ ፈንታ ሌብነትን ለመደ። ይባስ ብሎም የአሳዳሪውን (የፊልሞናን) ገንዘብ ሠርቆ ወደ ሮም ጠፍቶ ተመለሰ። ቅዱስ ፊልሞናም ለገንዘቡ ሳይሆን ለሕይወቱ አዘነ።
ያ ሠርቆ የጠፋው አገልጋይ ግን በሮም ከተማ ሲመላለስ ስብከተ ወንጌልን ይሰማል። ሰባኪው ደግሞ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነበር። ቁጭ ብሎ ሲማርም ልቡናው በርቶለት ተጸጸተ። ከሐዋርያውም ዘንድ ቀርቦ ኃጢአቱን ተናዞ ተጠመቀ።
ከዚያች ዕለት ጀምሮም ብርቱ ክርስቲያን ሆነ። በጥቂት ጊዜም የተጋ ሰባኪ፣ ርኅሩኅ እረኛ ሆነ። ፈጣሪውንም ደስ አሰኘ። ነገር ግን ስለ አንድ ነገር ፈጽሞ ያዝን ይተክዝም ነበር።
የድሮ አሳዳሪው ቅዱስ ፊልሞና እንዳዘነበት እያወቀ ዝም ማለት ባያስችለው ለመምህሩ ቅዱስ ጳውሎስ ነገረው። ያን ጊዜም ሐዋርያው በእሥራትና በግርፋት ይሰቃይ ነበር። በሮም ሳለም አጭር ክታብ (ደብዳቤን) ጽፎ ለዚህ ደቀ መዝሙሩ ሰጠውና ወደ ቀድሞ አሳዳሪው ወደ ፊልሞና ላከው።
ይህች ጦማር (ክታብ) ዛሬም ድረስ ከሰማንያ አንዱ አሥራው መጻሕፍት፣ ከቅዱስ ጳውሎስ አሥራ አራት መልእክታት አንዷ ሆና ተቆጥራ እንጠቀምባታለን። ክታቧ እጅግ አጭር ብትሆንም ምሥጢሯ ግን ሰፊ ነው።
ያ የተላከ ክርስቲያንም ያችን ክታብ ወስዶ ለቅዱስ ፊልሞና (ለቀድሞ አሳዳሪው) አስረከበ። ቅዱስ ፊልሞናም በደስታ አቅፎ ሳመው። ቀድሞውንም ያዘነ በወጣቱ አገልጋይ የነፍስ እዳ እንጂ በገንዘቡ አልነበረምና። ያ ተላኪ ሰውም በአካባቢው ሲያገለግል ቆይቶ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ተመልሷል። ደቀ መዝሙሩ ሆኖም ብዙ አገልግሏል።
በ፷፯ ዓ.ም ቅዱስ ጳውሎስ መሰየፉን ተከትሎ እርሱንም አሳድደው አሰቃይተው ጭኑን ሰብረው አሕዛብ ገድለውታል። በሰማይም የሐዋርያነትና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጅቷል።
(ጢሞ. ፬፥፮-፰ ፣ ፊልሞና ፩፥፩-፳፭)
አምላከ ቅዱሳን የአናሲሞስን መመለስ፣ ንስሐና በረከት ያድለን።
የካቲት ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አናሲሞስ ሐዋርያ
፪.አባ ዘካርያስ ዘሃገረ ስሃ
፫.አባ አካክዮስ ጻድቅ
፬.አባ ገብርኤል ሊቀ ጳጳሳት
፭.አባ ገብርኤል (የኢትዮጵያ ጳጳስ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም
፪.አበው ጎርጎርዮሳት
፫.አቡነ ምዕመነ ድንግል
፬.አቡነ አምደ ሥላሴ
፭.አባ አሮን ሶርያዊ
፮.አባ መርትያኖስ ጻድቅ
"ስለ ጽዮን ዝም አልልም።.....
አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ። የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።"
(ኢሳ ፷፪፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለጻድቁ አባታችን አባ መርትያኖስ ዓመታዊ የፍልሠት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አባ መርትያኖስ <3
አባ መርትያኖስ በበርሃ ከስልሳ ስምንት ዓመታት በላይ በቅድስና የኖሩ አባት ናቸው። ሰይጣን እርሳቸውን ፊት ለፊት ተዋግቶ መጣል ቢያቅተው በዝሙት በተለከፉ ሴቶች ያስቸግሯቸው ነበር።
አንድ ቀን አንዷ ሽቶ አርከፍክፋ በዝሙት ልትጥላቸው ብትል እግራቸውን እሳት ውስጥ ጨምረው እግራቸው እየተቃጠለ በሚወጣው ጠረን አጋንንትን አርቀዋል። እርሷንም በንስሐ መልሰው ለቅድስና አብቅተዋታል። ጻድቁ ከፈተና ለመራቅ በሃገራት መቶ ስምንት በዓቶች የነበሯቸው ብቸኛ አባት ናቸው።
ሶርያዊው ቅዱስ አባ መርትያኖስ ለስልሳ ስምንት ዓመታት በየበርሃው በጾምና በጸሎት፣ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ኑረዋል። በዝሙት የተለከፉ ሰዎችንም ወደ ቅድስና ሕይወት ጠርተው ብዙ አፍርተዋል።
በመጨረሻም በአቴና (Athens) ግሪክ ግንቦት ፳፩ ቀን ዐርፈው ተቀብረዋል። በዚህች ቀንም ወደ ሃገረ ሙላዳቸው ሥጋቸው ፈልሷል።
የካቲት ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ታላቁ አባ መርትያኖስ (በዝሙት ላለመሰናከል እግራቸውን በእሳት ያቃጠሉ አባት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፬.አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም
".....በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፤ ተፈተኑ። በመጋዝ ተሰነጠቁ። በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፮-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት <3
ቅዱሳን ነቢያት እጅግ ብዙ ናቸው። ከፈጣሪያቸው የተቀበሉት ጸጋም ብዙና ልዩ ልዩ ነው። ያም ሆኖ ከሁሉም ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ይበልጣል። መጽሐፍ እንደሚል ከእርሱም በፊት ቢሆን ከእርሱ በኋላ እንደ እርሱ ያለ ነቢይ አልተነሳምና።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ዓለም በተፈጠረ በሦስት ሺህ ስድስት መቶ ዓመት እስራኤል በረሃብ ምክንያት ሰባ አምስት ራሱን ወደ ምድረ ግብጽ ወረደ። በዚያም ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት ተከብረው ለሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት ደግሞ በባርነት በድምሩ ለአራት መቶ ሠላሳ ዓመታት በምድረ ግብጽ ኑረዋል።
በባርነት ዘመናቸውም 'ራምሴና ጋምሴ' የሚባሉ ሁለት ከተሞችን (ዛሬ ፒራሚዶች የምንላቸውን) ገንብተዋል። ግፋቸው እየበዛ ሲሔድ ግን ጩኸታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ። ያድናቸውም ዘንድ አንድ ቅዱስ ሰው እንዲወለድ አደረገ። ይህም ሰው ሙሴ ይባላል።
ወላጆቹ መታመናቸውን በፈጣሪያቸው ያደረጉ 'እንበረም' እና 'ዮካብድ' ሲሆኑ ከሌዊ ነገድ ናቸው። ከሙሴ ውጪም አሮንና ማርያምን ወልደዋል። ቅዱስ ሙሴ በተወለደበት ወራት ወንድ የእስራኤል ሕፃናት ይፈጁ ነበር። ጌታ ግን በገዳዮቹ ልቡና ርኅራኄን አምጥቶ አትርፎታል።
በኋላም በሦስት ወሩ ዓባይ ወንዝ ላይ ጥለውት ተርሙት (የፈርኦን ልጅ ናት።) ወስዳ በቤተ መንግሥት አሳድጋዋለች። 'ሙሴ' ያለችውም እርሷ ናት። ዕጓለ ማይ - እማይ ዘረከብክዎ (ከውኃ የተገኘ) ለማለት ነው። ወላጆቹ ያወጡለት ስም ግን 'ምልክአም' ይባላል። ገና ሲወለድ ፊቱ እንደ መልአክ ያበራ ነበርና።
ቅዱስ ሙሴ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ ፈርኦንን በጥፊ በመማታቱ ለፍርድ ቀርቦ እሳትን በመብላቱ አንደበቱ ኮልታፋ ሆኖ ቀርቷል። እናቱ ዮካብድ ሞግዚት ሆና ስላሳደገችው አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ የፈርኦንን ቤት ምቾትና የንጉሥ ልጅ መባልን ናቀ። ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው በአሕዛብ ቤት ካለ ምቾት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ሊቀበል ወዷልና።
(ዕብ. ፲፩፥፳፬)
አንድ ቀንም ለዕብራዊ ወገኑ ተበቅሎ ግብጻዊውን ገድሎት ወደ ምድያም ሸሸ። በዚያም ለአርባ ዓመታት የካህኑን ዮቶርን በጐች እየጠበቀ ኢትዮጵያዊቱን ሲፓራን አግብቶ ኖረ፤ ሁለት ልጆችንም አፈራ። ሰማንያ ዓመት በሞላው ጊዜ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ተናገረው። ሕዝቡንም ከባርነት ቀንበር እንዲታደግ ላከው።
ቅዱስ ሙሴም ከወንድሙ አሮንና ከአውሴ (ኢያሱ) ጋር ግብጻውያንን በዘጠኝ መቅሰፍት በአሥረኛ ሞተ በኩር መታ። እስራኤልንም ነጻ አወጣ። ሊቀ ነቢያት የሠራቸው ሥራዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም።
እርሱ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል።
ግብጻውያንን ከነ ሠረገሎቻቸው በባሕር ውስጥ አስጥሟል።
ለሕዝቡ መና ከደመና አውርዷል።
ውኃን ከጨንጫ (ከዓለት) ላይ አፍልቋል።
በብርሃን ምሰሶ መርቷቸዋል።
በሰባት ደመና ጋርዷቸዋል።
ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ነስቶላቸዋል።
ስለዚህ ፈንታ ግን ወገኖቹ ብዙ አሰቃይተውታል። እርሱ ግን ደግ፣ ቅንና የዋህ ሰው ነውና ብዙ ጊዜ ራሱን ለእነርሱ አሳልፎ ሰጥቷል። 'ሙሴሰ የዋህ እምኩሎሙ ደቂቀ እስራኤል' እንዲል።
(ዘኁ. ፲፪፥፫)
ቅዱስ ሙሴ ለአርባ ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ከእግዚአብሔር ጋር ለአምስት መቶ ሰባ ጊዜ ተነጋግሯል።
ከጸጋው ብዛትም ፊቱ ብርሃን ስለ ነበር ሰዎች እርሱን ማየት አይችሉም ነበር። ታቦተ ጽዮንንና አሥሩ ቃላትን ተቀብሎ ጽላቱ ቢሰበሩ ራሱ ሠርቶ በጌታ እጅ ቃላቱ ተጽፈውለታል።
'የቀረው የቅዱሱ ሕይወት በመጻሕፍተ ኦሪት (በብሔረ ኦሪት) ውስጥ የተጻፉ አይደሉምን?'
እኔ ግን ደካማ ነኝና ይህቺ ትብቃኝ። ቅዱስ፣ ክቡር፣ ታላቅ፣ ጻድቅ፣ ነቢይና ደግ ሰው ቅዱስ ሙሴ በመቶ ሃያ ዓመቱ ዐርፎ በደብረ ናባው ሊቃነ መላእክት ቅዱሳን ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሳቁኤል ቀብረውታል። መቃብሩንም ሠውረዋል።
(ይሁዳ. ፩፥፱)
አምላከ ሊቀ ነቢያት ደግነቱን አስቦ ከግራ ቁመት ከገሃነመ እሳት ይሰውረን። በረከቱንም አብዝቶ ያድለን።
የካቲት ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ (ሁለተኛው)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
፫.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
፬.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፭.አባ ገሪማ ዘመደራ
፮.አባ ጰላሞን ፈላሢ
፯.አባ ለትጹን የዋህ
"ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርኦን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ። ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና። ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና።"
(ዕብ ፲፩፥፳፬-፳፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
<3 ቅድስት ኤልሳቤጥ <3
በወንጌላዊው አንደበት የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ትውልዷ ከነገደ ሌዊ ነው። ሐረገ ሙላዷም ከቅዱስ አሮን ካህን ወገን ይመዘዛል። ከአሮን በቴክታና በጥሪቃ ወርዶ ሔርሜላ ላይ ይደርሳል።
ይህቺ ሔርሜላ የምትባል ደግ ሴት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ።) የሚባል የተባረከ ሰው አግብታ ሦስት ቡሩካት ልጆችን ወለደች። የመጀመሪያዋን "ማርያም" አሏት። እርሷ ቅድስት ሰሎሜን ወለደች። ሁለተኛዋን "ሶፍያ" አሏት። እርሷ ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደች። ሦስተኛዋ ግን የተለየች ናት፤ "ሐና" ብለው ሰየሟት። እርሷም የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ወለደች። በዚህም መሠረት ድንግል ማርያም፣ ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ሰሎሜ የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
ቅድስት ኤልሳቤጥ እድሜዋ በደረሰ ጊዜ ስም አጠራሩ የከበረ ደግ ካህን ለሆነ ለቅዱስ ዘካርያስ አጋቧት። እርሷ የሊቀ ካህናቱ ሚስት ናትና ክብሯ ከፍ ያለ ነበር። ምንም ልጅ ባይኖራትም ዘወትር በጸሎትና በጾም፣ ምጽዋትንም በማዘውተር፣ ነዳያንንም በማሰብ የምትኖር እናትም ነበረች።
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል።
"ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ።" ይላቸዋል።
(ሉቃ. ፩፥፮)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እነዚህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና የዘካርያስ ደግሞ መቶ ደርሶ ነበር።
ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው። ቅድስቲቷ መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች።
ድንግል እመቤታችን ወደ እርሷ መጥታ "ሰላም" ባለቻት ጊዜ ምንም ያሳደገቻት ልጇ ማለት ብትሆን መንፈስ ቅዱስ ስለ ሞላባት እመ ብርሃንን አመስግናታለች። ቡርክት፣ ብጽዕት፣ ከፍጥረተ ዓለሙ የከበረች መሆኗንም መስክራለች።
በማኅጸኗ ያለ የስድስት ወር ጽንስም የእመ አምላክን ድምጽ ቢሰማ በደስታ ዘሏል። ለፈጣሪውም ስግደተ ስባሔ አቅርቧል። ቅድስት ኤልሳቤጥ አክላም "ወምንትኑ አነ ከመ ትምጽኢ ኀቤየ እሙ ለእግዚእየ - የጌታዬ እናቱ ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይገባኛል?" ስትል በትሕትና ተናግራለች። ከጌታ እናት ጋር ለሦስት ወራት በአንድ ቤት ቆይታለች።
ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእስራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሄሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕፃን አለና እርሱንም ግደል።" አሉት።
እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል።
አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለሦስት (አምስት) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ አምስት (ሰባት) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት። ኤልሳቤጥ ማለት "እግዚአብሔር መሐላየ ነው።" አንድም "የጌታ አገልጋይ" ማለት ነው።
ሊቃውንትም፦
"ሰላም ለኤልሳቤጥ እንተ ወደሳ ወአልዓላ
ሉቃስ ወንጌለ ሶበ ጸሐፈ ለታኦፊላ
ሐገረ ይሁዳ አሜሃ ሶበ በጽሐት እምገሊላ።
ተሐሥየ በውስተ ከርሣ ወአንፈርዓጸ ዕጓላ
ለማርያም ድንግል ሶበ ሰምዓት ቃላ።" ሲሉ አመስግነዋታል።
ቸሩ መድኃኔ ዓለም ከእመቤታችን በረከተ ኪዳን አይለየን።
በዓሉንም የሰላም፣ የፍቅርና የበረከት ያድርግልን።
የካቲት ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የእመቤታችን አክስት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
፬.ቅዱስ ነዓኩቶ ለአብና ልጁ
፭.አቡነ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፪.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፫.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፬.አባ ዳንኤል ጻድቅ
"ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ። በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት። በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ 'አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ። የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮየ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈፀማልና ያመነች ብፅዕት ናት።' "
(ሉቃ ፩፥፵፩-፵፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ዘካርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ <3
ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፣ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ።
ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)
ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ።
ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል።
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ።
(ቅዳሴ ማርያም)
የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው። እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል።
ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ። እናንተ በድካማቸው ገባችሁ።" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል።
(ዮሐ. ፬፥፴፮)
ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፤ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ።" እንዳለ ጌታ በወንጌል።
(ማቴ. ፲፫፥፲፮ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ።
ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት፣ አራቱ ዐበይት ነቢያት፣ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ።
አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት፦
ቅዱስ አዳም አባታችን
ሴት
ሔኖስ
ቃይናን
መላልኤል
ያሬድ
ኄኖክ
ማቱሳላ
ላሜሕ
ኖኅ
አብርሃም
ይስሐቅ
ያዕቆብ
ሙሴና
ሳሙኤል ናቸው።
አራቱ ዐበይት ነቢያት፦
ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
ቅዱስ ኤርምያስ
ቅዱስ ሕዝቅኤልና
ቅዱስ ዳንኤል ናቸው።
አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት፦
ቅዱስ ሆሴዕ
አሞጽ
ሚክያስ
ዮናስ
ናሆም
አብድዩ
ሶፎንያስ
ሐጌ
ኢዩኤል
ዕንባቆም
ዘካርያስና
ሚልክያስ ናቸው።
ካልአን ነቢያት ደግሞ፦
እነ ኢያሱ
ሶምሶን
ዮፍታሔ
ጌዴዎን
ዳዊት
ሰሎሞን
ኤልያስና
ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው።
ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ።
የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እስራኤል)ና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ።
በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦
ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)፣
ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)፣
ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ።
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ።
ቅዱስ ዘካርያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፬፻፶ ዓ.ዓ አካባቢ ነው። "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው። አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል።
ነቢዩ ቅዱስ ዘካርያስ፦
ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት የነበረ፣
በጻድቅነቱ የተመሰከረለት፣
አሥራ አራት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት የተናገረ፣
ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በስፋት የተነበየ ነቢይ ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትም አንዱ ነው።
የአባታችን በረከት ይደርብን።
የካቲት ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ (ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ)
፪.ቅዱስ አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ (ከጻድቅነቱ ባሻገር በግብጽ በርሃ የሚኖሩ የብዙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት የጻፈ አባት)
፫.ቅዱሳን አርብዐ ሐራ ሰማይ (አርባ የሰማይ ጭፍሮች - ለአርባ ቀናት ሰብስጥያ በምትባል ሃገር መከራ ተቀብለው በሰማዕትነት ያለፉ ክርስቲያን ጓደኛሞች።)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፫.ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ
፬.ቅድስት እንባ መሪና
፭.ቅድስት ክርስጢና
"የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 'ወደ እኔ ተመለሱ.....እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።' "
(ዘካርያስ ፩፥፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለማር ፊቅጦር እና ቅዱስ አውሳብዮስ ካልዕ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ማር ፊቅጦር <3
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደማቸውና በገድላቸው ያስጌጡ ብዙ ሰማዕታት አሉ። ነገር ግን ከኮከብም ኮከብ ይበልጣልና ማን እንደ ጊዮርጊስና እስጢፋኖስ! ከእነርሱ ቀጥለው ከሚጠሩ ሰማዕታት ደግሞ አንዱና ዋነኛው ቤተ ክርስቲያን "ማር" የምትለው ቅዱስ ፊቅጦር ነው።
እስኪ ከበዛው መዓዛ ገድሉ ጥቂት እንካፈል።
ቅዱስ ፊቅጦር አባቱ ኅርማኖስ ይባላል። አረማዊና ጨካኝ ነው። እናቱ ግን የተመሰገች ቅድስት ማርታ ትባላለች። ልጇን እንደሚገባ አሳድጋው ሃያ ዓመት ሲሞላው የአንጾኪያ ንጉሥ፣ የሠራዊት አለቃና በመንግሥቱ ሦስተኛ አድርጐ ሾመው።
የድሮዋ አንጾኪያ (ሮም) እንደ ዛሬዋ አሜሪካ ዓለምን የተቆጣጠረች ሃገር ነበረች። ቅዱስ ፊቅጦር ደም ግባቱ ያማረ በጦርነትም ኃይለኛ ስለ ነበር ሁሉ ያከብሩት ይወዱትም ነበር::
እርሱ ግን ቀን ቀን ሲጾም ነዳያንን ሲያበላ ይውል ነበር። ሌሊት ደግሞ እኩሉን ሲጸልይና ሲሰግድ እኩሉን የእስረኞችን እግር ሲያጥብ ያድር ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆንኮ እርሱ የንጉሡ ሦስተኛ የሠራዊትም አለቃ ነው። በዘመኑ የሚያገድፍ ምግብና የወይን ጠጅ በአፉ ዙሮ አያውቅም።
ከነገር ሁሉ በኋላ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ካደ። ዘመነ ሰማዕታትም ጀመረ። አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ። ከአርባ ሰባት ሚሊየን በላይ ክርስቲያኖች በመንኮራኩር ተፈጩ። በመጋዝ ተተረተሩ። ለአራዊት ተሰጡ። በግፍም ተጨፈጨፉ። ቀባሪ አጥተውም ወደቁ።
በዚህ ጊዜ ማር ፊቅጦር እናቱን ቅድስት ማርታን በዕንባ ተሰናብቶ ወደ ንጉሡ ቀርቦ በክርስቶስ ስም ታመነ። ክፉ አባትም በልጁ ላይ ሞትን መከረ።
ከዚያም ቅዱሱን አፉን በብረት ለጉመው ወደ ምድረ ግብጽ አወረዱት። መሪያቸው እንዳልነበረ ወታደሮቹ መኳንንቱ ሁሉ ተዘባበቱበት። እርሱ ከምድራዊ ንግሥና ሰማያዊ መንግሥትን በሰዎች ፊት ከመክበር ስለ ክርስቶስ ሲል መናቅን መርጧልና።
ለቀናት፣ ለወራትና ለዓመታት መኳንንቱ እየተፈራረቁ አሰቃዩት። በእርሱ ላይ ያልሞከሩት የስቃይ ዓይነት አልነበረም። አካሉን ቆራርጠዋል ዓይኖቹን አውጥተዋል፤ ምላሱንም ቆርጠዋል። ሚያዝያ ፳፯ ቀን ግን በሰይፍ አንገቱን ቆርጠውታል። ስለዚህም እናት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ማክበር ታከብረዋለች።
እግዚአብሔርም ለቅዱስ ፊቅጦር እንዲህ አለው፦ "እንደ አቅሙ ስምህን የጠራ፣ መታሠቢያህን ያደረገ፣ ስምህን ያከበረ፣ የብርሃን ልብስ አጐናጽፌ ወደ መንግሥተ ሰማያት አስገባዋለሁ።"
ይህች ቀን ማር ፊቅጦር የተወለደባት ናት።
እናቱን ቅድስት ማርታ (ሶፍያንም) እናስባለን።
<3 ቅዱስ አውሳብዮስ ካልዕ (ጥዑመ ዜና) <3
ቅዱስ አውሳብዮስ በወጣትነቱ ከተባረከች ሚስቱ ጋር በድንግልና የኖረ፣
በዘመኑ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ ይጸልይ አራት ሺህ አቡነ ዘበሰማያት በአንድ ቀን ያደርስ የነበረ፣
ስለ ሃይማኖትም በቀስት የተወጋ፣ በእሳት የተቃጠለ፣ አካሉን ቆራርጠው የጣሉትና እግዚአብሔር ከሞት ያስነሳው ጻድቅና ሰማዕት ነው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ከነሥጋው ወደ ሰማይ ተነጥቆ ለአሥራ አራት ዓመታት ቆይቷል። ወደ ምድርም ተመልሶ ለአርባ ዓመታት በሐዋርያነት ከሰማንያ አምስት ሺህ በላይ አሕዛብን ወደ ሃይማኖት መልሷል።
ጌታም "በስምህ የተማጸነውን እስከ ሰባት ትውልድ እምርልሃለሁ ብሎታል።"
አባቶቻችን ደግሞ 'ስም አጠራሩ የከበረ ዜና ሕይወቱ ያማረ' ሲሉ ይጠሩታል።
የቅዱሳኑን በረከት ያድለን።
የካቲት ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት (ልደቱ)
፪.ቅዱስ አውሳብዮስ ጻድቅ (ጥዑመ ዜና)
፫.ቅዱስ ሰርግዮስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ መፁን ቀሲስ
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (የቅዱስ ፋሲለደስ ልጅ)
፮.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት
፯.አባ ክፍላ
፰.አባ ኅብስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬.ቅዱስ አስከናፍር
፭.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ
"እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና። በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።"
(ዕብ ፮፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱሳን አባቶቻችን ዓመታዊ የጉባዔ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ጉባዔ አሞር <3
የቀደሙት ደጋግ ሊቃውንት ኒቅያ፣ ቁስጥንጥንያና ኤፌሶንን በመሰሉ ከተሞች ጉባዔ ሠርተው መናፍቃንን ረትተው ቤተ ክርስቲያንን አጽንተው አልፈዋል። ከሦስቱ ጉባዔያት ውጪ ደግሞ በየጊዜው ለተነሱ መናፍቃን አካባቢያዊ ጉባዔዎችን አድርገዋል።
ከእነዚህም አንዱ በዛሬው ዕለት የተደረገው ሲሆን መካነ ጉባዔው አሞር የሚባል ደሴት ነበር። በወቅቱ አንዳንድ ስኁታን ክርስትናን ከይሁዲ እምነት ጋር ለማጣመር ባደረጉት ጥረት ችግር በመከሰቱ በጊዜው የነበሩ ጳጳሳትና ሊቃውንት ጉባዔ ሠርተው መናፍቃኑን ተከራክረው ረትተው ለተመለሱት ንስሐ ሰጥተው እንቢ ያሉትን አውግዘው ተለያይተዋል።
አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።
መጋቢት ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.የቅዱሳን ሊቃውንት ጉባዔ (አሞር ደሴት ውስጥ)
፪.ቅዱስ ሐኑልዮስ መኮንን (ሰማዕት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ (ወንጌላዊው)
፪.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)
"ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።"
(ሐዋ ፳፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት <3
ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሃገሩ ሮሃ (ሶርያ አካባቢ) ሲሆን ረዓዬ ኅቡዓት (ምሥጢራትን የተመለከተ) ይባላል።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ሃገር ይህ ቀረው የማይባል ኃጢአተኛ ሰው ነበር። ታዲያ ምንም ኃጢአተኛ ሰው ቢሆን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍፁም ልቡ ይወዳት ነበርና በመዳን ቀን ጥሪ ለንስሐ አበቃችው።
ከዚያች ዕለት ጀምሮም ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው፣ ንጹሕ የቤተ ክርስቲያን መስዋዕት፣ ጽኑዕ የበርሃ ምሰሶ ሆነ። ድንግል እመቤታችንም ከነሥጋው ወደ ሰማያት ወስዳ ገነትና ሲዖልን አሳይታ ከአዳም፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴና ዳዊትን ከመሰሉ ቅዱሳን ጋር አስተዋውቃ ከዚህም በላይ የሆነና በሰብአዊ አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢር አሳይታ ወደ ምድር መልሳዋለች።
ቅዱስ ጐርጐርዮስ በሰማይ (በገነት) በነበረው ቆይታ ክብረ ቅዱሳንን ተመልክቶ አድንቋል። በተለይ በፍጹምነት ድንግልናቸውን የጠበቁ ቅዱሳንና ቅዱሳት ደናግል አኗኗራቸው ከአምላክ እናት ከሰማይ ንግሥት ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ጋር መሆኑን አይቷል።
"የለበሱት ልብስም በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የሚቻል አይደለም።" ይላል። የደናግል ፊታቸው ከፀሐይ ሰባት እጅ ያበራልና ግርማቸው ያስፈራል።
ቅዱሱ ሰው በዚያው በሰማይ ሳለ ደግሞ ይህንን ተመለከተ። አንድ አረጋዊ ጽሕሙ ተንዠርግጐ የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሶ ይመጣል። ቅዱሳን መላእክት በፊት በኋላ፣ በቀኝ በግራ ከበውት ሳለ እግዚአብሔርን ሊያመሰግን ጀመረ።
"እግዚኦ እግዚእነ ጥቀ ተሰብሐ ስምከ በዲበ ምድር - አቤቱ ጌታችን በምድር ሁሉ ስምህ የተመሰገነ ሆነ።" ሲል መላእክቱ በዝማሬ አጀቡት። በዚህ ጊዜም ታላቅ መናወጥ ሆነ። ደናግሉም የቅዱሱን ሽማግሌ በረከቱን ተሳተፉ።
ይህ አመስጋኝ ሽማግሌ ልበ አምላክ፣ ጻድቅ፣ የዋህና የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት ነበር። በምን ታወቀ ቢሉ፦
በበገናው፦ አንድም እመቤታችን "አባቴ ዳዊት!" ብላ ስትጠራው ጐርጐርዮስ ሰምቷልና።
በመጨረሻም እመቤታችንን በፍጹም ክብርና ግርማ ተመልክቷት ሐሴትን አድርጓል። እመ ብርሃንም "ተወዳጅና ንጹሕ ሰው ነህ።" ስትል ቅዱስ ጐርጐርዮስን አመስግናዋለች። ስለዚህ ዓለምም እንዲህ የሚል መልእክትን ልካለች።
"ልጆቼ ሆይ! ከብርሃን ጨለማን፣ ከደግነት ክፋትን፣ ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን ምነው መምረጣችሁ? እኔ ስለ እናንተ በየቀኑ እየለመንሁ እነሆ አለሁ። ወደ ጨለማ ገሃነም እንዳትወርዱ እባካችሁ ንስሐ ግቡ!"
ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ለቅዱሱ ሰው ነግራው ቅዱስ ዳዊትን አስከትላ በግሩማን መላእክት ታጅባ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት (የእሳት መጋረጃዎች ወደ ተተከሉበት ድንኳን) ገባች፤ በዚያም ተመሰገነች።
ለዚያም አይደል ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
"ይዌድስዋ መላእክት ለማርያም በውስተ ውሳጤ መንጦላዕት ወይብልዋ በሐኪ ማርያም ሐዳስዩ ጣዕዋ።" ሲል ያመሰገናት።
ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከሰማይ ቆይታ መልስ ያየውን ሁሉ ጽፎ ለአበው ሰጥቷል። ስለዚህም ረዓዬ ኅቡዓት (ምሥጢራትን ያየ) ይሰኛል። ቅዱሱ ተረፈ ዘመኑን በተጋድሎ ፈጽሞ በዚህች ቀን አርፏል።
የቅዱሱ እመቤት ድንግል እመ ብርሃን መዓዛ ፍቅሯን ታብዛልን።
መጋቢት ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት (ዘሃገረ ሮሃ)
፪.አቡነ መክፈልተ ማርያም ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
፫.አባ መከራዊ ዘሃገረ ኒቅዮስ (አረጋዊ፣ ጻድቅ፣ ጳጳስና ሰማዕት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፬.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፭.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
፮.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፯.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
"ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው። ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ። ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።"
(፩ጢሞ ፩፥፲፭-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ነቢይና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ <3
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል፦ "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ።" ይላቸዋል።
(ሉቃ. ፩፥፮)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እነዚህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና የዘካርያስ ደግሞ መቶ ደርሶ ነበር።
ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው።
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች።
በስድስተኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ ሰኔ ፴ ቀን ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል።
ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእስራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሄሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕፃን አለና እርሱንም ግደል።" አሉት።
እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል። አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለሦስት (አምስት) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ አምስት (ሰባት) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት።
ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው። እርሷም ስደት ላይ ነበረችና። ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው። ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው። ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ።" አላት። ባርካው አጽናንታውም ተለያዩ።
ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ። ለሃያ አምስት (ሃያ ሦስት) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም። ይህችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም።
ከዚህ በኋላ ሠላሳ ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው፦ "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ።" አለው። ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና።
(ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩)
አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ።" ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና።
(ሉቃ. ፩፥፸፮)
ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ። ያዩት ሁሉ ፈሩት፤ አከበሩት። ቁመቱ ቀጥ ያለ፣ ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ፣ ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ፣ መልኩ የተሟላ፣ ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና።
ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ። ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው። በዚህ አገልግሎት ለስድስት ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ፤ የሚገባበትም ጠፋው።
"እንቢ ጌታዬ! አንተ አጥምቀኝ?" አለው። ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው፤ አጠመቀው። በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል።
ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሄሮድስን ገሰጸው፤ ንጉሡም ተቀይሞ ለሰባት ቀናት አሠረው። ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሄሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው። እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት። አበው "እምሔሶ ለሄሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሄሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር።" ይላሉ። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል።
(ማቴ. ፫፥፩ ፣ ማር. ፮፥፲፬ ፣ ሉቃ. ፫፥፩ ፣ ዮሐ. ፩፥፮)
ርጉም ሄሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች። ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት።
ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ሥልጣን ሰጥቶ አሰናበታት። በመላው ዓለም ለአሥራ አምስት ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዐርፋለች።
በዚህች ዕለትም በልሑክት (በሸክላ ዕቃ) የተገኘችበት በዓል ይከበራል። በዓሉም "ተረክቦተ ርዕሱ" በመባል ይታወቃል።
"አስማተ ዮሐንስ መጥምቅ - የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች"
፩.ነቢይ
፪.ሐዋርያ
፫.ሰማዕት
፬.ጻድቅ
፭.ካህን
፮.ባሕታዊ (ገዳማዊ)
፯.መጥምቀ መለኮት
፰.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
፱.ድንግል
፲.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
፲፩.ቃለ ዓዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
፲፪.መምህር ወመገሥጽ
፲፫.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)
ጌታችን መድኃኔ ዓለም ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ብሎ ይቅር ይበለን። ጸጋውን፣ በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን።
የካቲት ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.አቡነ ሙሴ ዘገርዓልታ
፫.አባ ሚናስ ሊቀ ጳጳሳት
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
፪.አባ ሣሉሲ ክቡር
፫.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
"ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ።.....
ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን።.....
እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም።.....
ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ። ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።"
(ማቴ ፲፩፥፯-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ቴዎድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ቴዎድሮስ ዘሮም <3
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቅዱሱ ሊቅ) በመጽሐፈ ሰዓታት ሰማዕታትን፦
"መስተጋድላን ከዋክብት ብሩሃን
ማኅትዊሃ ለቤተ ክርስቲያን።" ይላቸዋል።
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮም መንግሥት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር። የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግሥቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ፦ ፋሲለደስ፣
ገላውዴዎስ፣
ፊቅጦር፣
መቃርስ፣
አባዲር፣
ቴዎድሮስ (ሦስቱም)፣
አውሳብዮስ፣
ዮስጦስ፣
አቦሊና ሌሎቹም ነበሩ።
ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ፦
ማርታ፣
ሶፍያ፣
ኢራኢ፣
ታኡክልያና ሌሎቹም ነበሩ። ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር። ወቅቱ ከፋርስ፣ ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ (ሞተ)።
የሮም መንግሥትም ባዶ ሆነች። ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር። ግን እነርሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ።
በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪጳዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር። ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪጳዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው። ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው።
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም። የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው። ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው። ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች።
ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ። የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ። ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው። ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግሥት እንምረጥ።" አላቸው። ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ።
ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ ይጸልዩ ገቡ። ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር። ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው። ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ።
አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ - ቤተ ክርስቲያኖች ይዘጉ፤ ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ።" አለ። አጵሎን፣ አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ።
በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ።
ምድር በደም ታጠበች።
ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ።
እኩሉ ተገደለ።
እኩሉ ተቃጠለ።
እኩሉ ታሠረ።
እኩሉም ተሰደደ።
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም። ይልቁኑ እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው፣ እንደ ብዕር አጥንታቸው፣ እንደ ብራና ቆዳቸው ሆኖ ተጽፏል እንጂ። ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው።
ስለዚህም "ተጋዳዮች፣ የሚያበሩ ኮከቦች፣ የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለው እነርሱ እየቀለጡ አብርተዋል። ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ፻፶ እስከ ፫፻፲፪ ዓ/ም ድረስ ያለው ዘመን ነው።
በተለይ ግን ከ፪፻፸ዎቹ እስከ ፫፻፲፪ ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና። የአርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል። የሰማዕታት ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል፣ የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም።
(ማቴ. ፲፥፲፮ ፣ ማር. ፲፫፥፱ ፣ ሉቃ. ፲፪፥፬ ፣ ዮሐ. ፲፮፥፩ ፣ ሮሜ. ፰፥፴፭ ፣ ራእይ. ፪፥፱)
የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ነው።
ቅዱስ ቴዎድሮስ በዘመነ ሰማዕታት (በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ከተነሱ ታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው። በወቅቱ መሪ የነበረው ክሀዲው መክስምያኖስ "ክርስቶስን ክደህ ለጣኦት ስገድና በከተማዋ ላይ እሾምሃለሁ።" ቢለው "ለእኔ ሃብቴም ሹመቴም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።" በማለቱ ንጉሡ ተቆጥቶ በብረት ዘንግ አስደበደበው። በመንኮራኩር አበራየው። ለአናብስት ጣለው። አካላቱን ቆራረጠው። በእሳትም አቃጠለው። ቅዱስ ቴዎድሮስ ስቃዮችን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በትዕግስት ተቀበለ። በፍጻሜውም አንገቱን በሰይፍ ተመትቶ ሦስት አክሊላት ወርደውለታል።
ከፈጣሪው ዘንድም ነጭ መንፈሳዊ ፈረስና ቃል ኪዳን ተቀብሏል። ስሙን የጠራ፣ መታሠቢያውን ያደረገ ዋጋው አይጠፋበትም።
(ማቴ. ፲፥፵፩)
አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከት ይክፈለን። አይተወን፣ አይጣለን፣ ጾሙንም ለበረከት ያድርግልን።
የካቲት ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
፪.ስድስት ሺህ ሦስት መቶ አራት ሰማዕታት (በቅዱስ ቴዎድሮስ አምላክ አምነው ሰማዕትነት የተቀበሉ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
"እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን።"
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. ፸፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሆሴዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ <3
ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፣ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ።
ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)
ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ።
ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል።
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ።
(ቅዳሴ ማርያም)
የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው። እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል።
ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ። እናንተ በድካማቸው ገባችሁ።" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል።
(ዮሐ. ፬፥፴፮)
ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፤ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ።" እንዳለ ጌታ በወንጌል።
(ማቴ. ፲፫፥፲፮ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲)
ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ።
ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት፣ አራቱ ዐበይት ነቢያት፣ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ።
አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት፦
ቅዱስ አዳም አባታችን
ሴት
ሔኖስ
ቃይናን
መላልኤል
ያሬድ
ኄኖክ
ማቱሳላ
ላሜሕ
ኖኅ
አብርሃም
ይስሐቅ
ያዕቆብ
ሙሴና
ሳሙኤል ናቸው።
አራቱ ዐበይት ነቢያት፦
ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
ቅዱስ ኤርምያስ
ቅዱስ ሕዝቅኤልና
ቅዱስ ዳንኤል ናቸው።
አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት፦
ቅዱስ ሆሴዕ
አሞጽ
ሚክያስ
ዮናስ
ናሆም
አብድዩ
ሶፎንያስ
ሐጌ
ኢዩኤል
ዕንባቆም
ዘካርያስና
ሚልክያስ ናቸው።
ካልአን ነቢያት ደግሞ፦
እነ ኢያሱ
ሶምሶን
ዮፍታሔ
ጌዴዎን
ዳዊት
ሰሎሞን
ኤልያስና
ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው።
ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ።
የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እስራኤል)ና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ።
በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦
ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)፣
ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)፣
ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ።
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ።
ቅዱስ ሆሴዕ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፰፻ ዓ.ዓ አካባቢ ነው። "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው። አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል።
ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ሆሴዕ 'ዖዝያ' በመባልም ይታወቃል። ቅዱሱ ነቢይ የቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል ባልንጀራ የነበረ ሲሆን በአራት ነገሥታት ዘመን (ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ደጉ ሕዝቅያስ) ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናግሯል። የትንቢት ዘመኑም ከሰባ ዓመት በላይ ነው።
ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሆሴዕ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራም በስፋት ተንብዩዋል። አሥራ አራት ምዕራፎች ያሉት የትንቢቱ ጥራዝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ሆሴዕ ማለት መድኃኒት ማለት ነው። የመዳን ትምህርትንና ትንቢትን ሊናገር ተመርጧልና።
ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ፣ በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን። ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን።
የካቲት ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ (ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት)
፪.ቅዱስ ሳዶቅ ሰማዕት
፫.ሁለት ሺህ ስምንት ሰማዕታት (ከቅዱስ ሳዶቅ ጋር የተሰየፉ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
"ኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንመለስ። እርሱ ሰብሮናልና እርሱም ይፈውሰናል። እርሱ መትቶናል እርሱም ይጠግነናል። ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል። በሦስተኛውም ቀን ያስነሳናል። በፊቱም በሕይወት እንኖራለን። እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ እንከተል።"
(ሆሴዕ ፮፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለአባታችን ቅዱስ አጋቢጦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ አጋቢጦስ <3
ቅዱስ አጋቢጦስ፦
ይህንን ዓለም ንቆ ለበርካታ ዘመናት በፍፁም ምናኔ የኖረ፣
ምድራዊ ሃብትና ሹመት ሞልቶለት ሳለ ከሁሉ የክርስቶስን ፍቅር የመረጠ፣
ከደግነቱ ብዛት የተነሳ ምግብ ሲያዘጋጅ ሽምብራውን ከክቶ ለሌሎች ከሰጠ በኋላ ለራሱ የሚመገበው ገለባውን (አሠሩን) ነበር።
ሌሊቱን በጸሎት ለመትጋት ማታ ማታ አመድ ይመገብ ነበር። በዚህም ቅዱስ ዳዊት "አመድን እንደ እህል በላሁ።" ያለው በዚህ ቅዱስ ሕይወት ላይ ተገልጧል።
(መዝ. ፻፩፥፱)
ቅዱስ አጋቢጦስ በዘመኑ ከሠራቸው ይህኛው እጅግ ይገርመኛል። እርሱ በበርሃ እያለ ዘመኑ የሰማዕታት በመሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች በርጉማን መክስምያኖስና ዲዮቅልጢያኖስ ተገድለዋል። ቅዱሱን ግን በአካባቢው የነበረ ሃገረ ገዢ ከበዓቱ አስወጥቶ ወደ ውትድርና ሥራ አስገብቶታል።
ሰይጣን በዚህ ከተጋድሎና ከቅድስና ሕይወት እንደሚያርቀው ተማምኖ ነበር። ቅዱስ አጋቢጦስ ግን በወታደሮች መካከል ሆኖም ተጋድሎውን ቀጠለ። የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ቢሾሙትም እርሱ ከበጐ ማንነቱ ፈጽሞ አልተለወጠም።
ክርስቲያን ማለት እንዲህ ነውና። ክርስትና ሲመቸን፣ ሲመቻችልን፣ በአጋጣሚ ወይም በምክንያት የምንኖረው ሕይወት አይደለም። ፍጹም ፍቅር የጊዜ፣ የቦታ፣ የሁኔታ ገደብ የለውምና አባቶቻችን በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጸንተው ክርስቶስ መድኃኒታችንን አስደሰቱ።
ከቅዱስ ጳውሎስ ጋርም እንዲህ ሲሉ ዘመሩ፦ "መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ - ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል!"
ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አጋቢጦስ ለዘመናት ሰው ሳይገድል ፈጣሪውን ሳይበድል ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከምጽዋትና ትሕርምት ሳይጐድል ኖረ። በዚህም ሰይጣንን አሳፈረ። ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ።
በዚህ ጊዜም ወደ በዓቱ ለመመለስ መንገድን ይፈልግ ይጸልይም ገባ። እግዚአብሔርም ወደ በርሃ የሚመለስበትን መንገድ በቸርነቱ አቀናለት።
ነገሩ እንዲህ ነው፦
ዘመነ ሰማዕታት አልፎ ራትዕ (የቀና) ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ነገሠ። ስደት ቆመ፤ የታሠሩ ተፈቱ፤ አብያተ ክርስቲያናት ታነጹ። ለክርስቲያን ቀደምቶቻችንም ታላቅ ተድላ ሆነ።
ጊዜው ለሁሉ ክርስቲያን የተድላ ቢሆንም አንድ ወጣት በደዌ ሰይጣን ያሰቃየው ነበር። ወጣቱ የንጉሡ የቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ባለሟል፣ ባለብዙ ሃብት፣ መልኩ ያማረ ነውና ሁሉ ያዝንለታል። ይልቁኑ ቅዱሱ ንጉሥ ተጨነቀለት።
አንድ ቀን ግን ከወታደሮቹ አንዱ ያን ወጣት "አንተንኮ አጋቢጦስ ይፈውስህ ነበር።" ይለዋል። ወጣቱ ግን አላወቀምና "ከመቼ ወዲህ የጦር አለቃ እንዲህ አድርጐ ያውቃል?" ሲል በጥያቄ ይመልስለታል። ወታደሩ ግን ቀስ አድርጐ ምሥጢሩን ይነግረዋል።
ይህ ነገር ሲያያዝ ከንጉሡ ደርሶ ቅዱስ አጋቢጦስን አስጠርቶ "እባክህ ፈውስልኝ?" ይለዋል። "ካዳንክልኝም የፈለግኸውን አደርግልሃለሁ።" ሲል ያክልለታል። ቅዱስ አጋቢጦስም ወደ ፈጣሪው ለምኖ ሰይጣንን ይገስጸዋል። በቅጽበትም በክርስቶስ ኃይል ወጣቱ ይድናል።
ቅዱስ ቆስጠንጢኖስም ከደስታው ብዛት "ምን ላድርግልህ?" ቢለው ቅዱሱ "ከሹመቴ ሻረኝ፤ ወደ በርሃ አሰናብተኝ።" ብሎ መሻቱን ገለጸለት። ቅዱሱ ንጉሥም በመገረም ቡራኬውን ተቀብሎ ወደ በርሃ ሸኝቶታል።
ወገኖቼ! በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊው እርከን ሥልጣንን የሚንቁ ሰዎችን ካላገኘን መፍትሔው ሩቅ ነው። እኛም ከሥልጣን መሻት እንራቅ። ማር ይስሐቅ እንደ ነገረን ሰይጣን ያደረበት ሰው ሹመትን (ሥልጣንን) በመሻቱ ይታወቃልና።
ቅዱሱ በፍፃሜ ዘመኑ እረኝነት (ጵጵስና) ተሹሞ ብዙ ኢ-አማንያንን ወደ ክርስትና መልሶ፣ ድውያንን ፈውሶ፣ እውራንን አብርቶ፣ በርካታ ተአምራትንም አድርጎ በዚህች ቀን አርፏል።
ልመናው በረከቱ ይደርብን።
የካቲት ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤጲስቆጶስ)
፪.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት (ዘጋዛ)
፫.ቅዱስ ሚናስ ዘቆጵሮስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምህረ ትሩፋት)
፪.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፫.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
፬.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮.ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል)
"የሚያሳድዷችሁን መርቁ።.....
ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ። ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ። የትዕቢትን ነገር አታስቡ። ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ።"
(ሮሜ ፲፪፥፲፬-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን አደረሳችሁ!
‹‹ኦ ፍጡነ ረድኤት እምሩጸተ ነፋስ
ወዐውሎ ለዘይጼውዓከ በተወክሎ
ጊዮርጊስ ቅረብ ለምሕረት ወለተሣህሎ፡፡
ተወከፍ ወትረ ጸሎትየ ወቃለ ጽራኅየ ኵሎ፡፡ እስመ ልበ አምላክ ርኅሩኅ በኀቤከ ሀሎ፡፡››
"ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! አንተን በመታመን ለጠራህ ሁሉ ፈጥነህ ስትደርስለት ከዓውሎ ነፋስ ይልቅ በተፋጠነ ሩጫ ነው እኮን፡፡
ጊዮርጊስ ሆይ! የዘወትር ጸሎቴንና የቃሌንም የልመና ጩኸት ትቀበል ዘንድ ለይቅርታና ለምሕረት ፈጥነህ ወደ እኔ ቅረብ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
እንኳን ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሐዋርያ እና ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት <3
በዚህች ዕለት በ፲፰፻፹፰ ዓ.ም በቅዱስ ጊዮርጊስ ምልጃና ረዳትነት አባቶቻችን አድዋ ላይ ጣልያንን ድል አድርገዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ደጉን ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን እናስባቸው ዘንድ ይገባል።
<3 ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሐዋርያ <3
ቅዱስ ፖሊካርፐስ፦
ከ፸ እስከ ፻፶፮ ዓ.ም ድረስ የነበረ፣
ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ ከመሰከረላቸው ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ (የሰርምኔስ) ጳጳስ የነበረ፣
ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቃል በቃል የተማረና ደቀ መዝሙሩ የነበረ አባት ነው።
ታላቁ አግናጥዮስ (ምጥው ለአንበሳ) የዚህ ቅዱስ ባልንጀራ ነበር። ከአርባ ስድስት ዓመታት በላይ በፍፁም ትጋት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎ አረማውያን በሰማንያ ስድስት ዓመቱ በአደባባይ በእሳት አቃጥለው ገድለውታል። አባቶቻችን "ሐዋርያዊ" ሲሉ ይጠሩታል።
<3 ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት <3
በቤተ ክርስቲያን ስመ ጥር ከሆነ ቅዱሳን ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ አውሳብዮስ ነው። ተወልዶ ያደገው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) ሲሆን ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። አባቱ ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፋሲለደስ ነው። እናቱም ቡርክት ሶፍያ ትባላለች።
ሰማዕቱ ቅዱስ መቃርስ ትንሽ ወንድሙ መሆኑም ይታወቃል። ቅዱሳን እነ ፊቅጦር፣ ገላውዴዎስ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮስጦስ፣ አባዲር ባልንጀሮቹ ሆነው ኑረዋል።
ቅዱስ አውሳብዮስ የቅዱስ ፋሲለደስ ፍሬ ነውና ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር ሆነ። በቤተ መንግሥት ውስጥ ስንት የተደላደለና የተቀማጠለ ነገር እያለ እርሱ ግን እንደ ቡሩክ አባቱ ንጽሕናን መረጠ። የወርቅ ካባ ደርቦ ሲሰግዱ ማደር ምን ይደንቅ!
ያ ዘመን እጅግ ግሩም የሆኑ ቅዱሳን በቤተ መንግሥት የታዩበት ነበር። ቅዱስ አውሳብዮስ በምጽዋት፣ በጾምና ጸሎት የሚኖር ቢሆንም በየጊዜው ወደ ጦርነት ይላክ ነበር። ምክንያቱም እርሱ ኃያል የጦር ሰው የሠራዊቱም ሁሉ አለቃ ነውና። በሔደበት ሁሉም በእግዚአብሔር ኃይል ድል ያደርግ ነበር።
አንድ ጊዜም ከፋርስ ቁዝ ሰዎች ጋር ጦርነት ውስጥ ገቡ። ይህንን ጦርነት በበላይነት እንዲመሩ ቅዱሳን አውሳብዮስና ዮስጦስ በኑማርያኖስ (ንጉሡ ነው።) ተሹመው ወደ ሠልፍ ገቡ።
በጦርነቱ ጐዳና ላይ ሳሉ ግን አንድ አታላይ ሰላይ በጠላት እጅ እንዲወድቁ አደረጋቸው። የተማረኩና የታሠሩ ዮስጦስና ሠራዊቱ ሲሆኑ ቅዱስ አውሳብዮስ ይህን ሰምቶ አለቀሰ። ወደ ፈጣሪውም እየተማጸነ ለመነ።
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ አረጋጋው። ድል መንሳትንም ሰጥቶት አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ዮስጦስን አስፈታው። ጠላቶቻቸውንም እያሳደዱ አዋረዷቸው። "ወመጠውከኒ ዘባኖሙ ለጸርየ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ።
ከዚህ ሠልፍ በኋላ ቅዱሳን አውሳብዮስና ዮስጦስ በድል አድራጊነት ወደ አንጾኪያ ሲመለሱ ግን አንጀትን የሚቆርጥ ዜና ደረሳቸው። አምላከ አማልክት ክርስቶስ ተክዶ ጣዖታት (እነ አጵሎን፣ አርዳሚስ) እየተሰገደላቸውም ደረሱ። ይህንን ያደረገ ደግሞ የሰይጣን ታናሹ የሆነ ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ነው።
ቅዱሳኑንም ለጣዖት ስገዱ ሲል በአደባባይ ጠየቃቸው። ድፍረቱ ያናደደው ቅዱስ አውሳብዮስ ግን ሰይፉን መዞ ወደ ንጉሡ ተራመደ። ያን ጊዜ ንጉሡ ሸሽቶ ሲያመልጥ መሳፍንቱን ሜዳ ላይ በተናቸው። አባቱ ቅዱስ ፋሲለደስ ባይገለግለው ኖሮ ኃያል ነውና ባላተረፋቸው ነበር።
ከቀናት በኋላ ግን ቅዱስ አውሳብዮስ በጾምና ጸሎት ሰንብቶ ሰማዕት ለመሆን ልቡ ቆረጠ። ቅዱስ ሚካኤልና አባቱ ፋሲለደስም በምክር አበረቱት። እርሱም በአጭር ታጥቆ በከሐዲው ንጉሥ አደባባይ ላይ ቆመ።
"እኔ ክርስቲያን ነኝ። ክርስቶስን አመልካለሁ። ለእርሱም እገዛለሁ። ጣዖታት ግን ድንጋዮች ናቸውና አይጠቅሙም። የሚሰግድላቸውም የረከሠ ነው።" ሲል አሰምቶ ተናገረ። ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ እዚያው ሊገድለው ፈልጐ ነበር። ቅዱሱ ተወዳጅ ሰው ነበርና ሁከት እንዳይነሳ አውሳብዮስ ወደ አፍሪቃ (ግብጽ) ሒዶ እንዲገደል ተወሰነበት።
በምድረ ግብጽም አረማውያን በእሳትም፣ በግርፋትም፣ በስለትም ብዙ አሰቃዩት። ቅዱስ ሚካኤል ግን ገነትን አሳይቶ ከደዌው እየፈወሰ ተራዳው። በመጨረሻም በዚህች ቀን ገድለውት አክሊለ ክብርን ተቀዳጅቷል።
አምላከ ቅዱሳን ሰማዕታት ጽናታቸውን አድሎ ከበረከታቸው ይክፈለን።
የካቲት ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት (አባቶቻችንን አድዋ ላይ የረዳበት)
፪.ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሐዋርያዊ ሰማዕት (የሰርምኔስ ጳጳስ)
፫.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት (የቅዱስ ፋሲለደስ ልጅ)
፬.ቅዱስ አውስግንዮስ ሰማዕት
ወርኀዊ በዓላት
፩.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
፫.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፬.አባ ሳሙኤል
፭.አባ ስምዖን
፮.አባ ገብርኤል
"በሰርምኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል፦ 'መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ።.....
እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።"
(ራእይ ፪፥፰-፲)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለአቡነ አቢብ እና ለፋርስ ሰማዕታት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አቡነ አቢብ (አባ ቡላ) <3
ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን!
እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን፣ ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ ተሰኝተናል!
ቅዱሱ አባታችን "ቡላ - የእግዚአብሔር አገልጋይ" ብለን እንጠራሃለን።
ዳግመኛም "አቢብ - የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን።
እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን።
አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ!
ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን የተቀበለ!
ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን የሚያወርስ!
የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር፣ ምስጋናና ስግደት በጸጋ ይገባሃል እንላለን።
ልደት
አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት። ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ። ልጅ ግን አልነበራቸውም። ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ።
በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች። ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል።
"ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን"
ጥምቀት
ቅዱሱ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለአንድ ዓመት ቆየ። ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር። እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ 'አጥምቀው' አለችው።
ወደ በርሃ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕፃኑ ተነስቶ እጆቹን ዘርግቶ "አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ። ከሰማይም ሕብስትና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ጳጳሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው። የሕፃኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን።" ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው። እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ።
ሰማዕትነት
የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለአሥር ዓመታት አሳድገውት ድንገት ኅዳር ፯ ቀን ተከታትለው ዐረፉ። ሕፃኑን የማሳደግ ኃላፊነትን የአካባቢው ሰዎች ሆነ። ሕፃኑ ቡላ ምንም የአሥር ዓመት ሕፃን ቢሆንም ያለ ማቋረጥ ሲጾም ሲጸልይ ክፉ መኮንን "ለጣዖት ስገዱ።" እያለ መጣ።
በዚህ ጊዜ በሕፃን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ። በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት። በጅራፍ ገረፉት፣ በዘንግ ደበደቡት፣ ቆዳውን ገፈፉት፣ በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት። ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ሁለት ጊዜ ከሞት ተነሳ። በመጨረሻ ግን ሚያዝያ ፲፰ ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል።
ገዳማዊ ሕይወት
ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው። ከሰማዕታትም ጋር ደመረው። በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ። መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል?" ሲል ጌታን ለመነ።
ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል። ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ።" አለው። ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ ልብሰ መነኮሳትን አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው።
ተጋድሎ
አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዓርብ ዓርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ። ራሱን ይገርፋል፤ ፊቱን በጥፊ ይመታል፤ ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል፤ ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል።
በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል። ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል። ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለአርባ ሁለት ዓመታት ጹሟል። ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር።
የሚታየውም እንደ ተወለደ፣ እንደ ተጠመቀ፣ እንደ ተሰቀለ፣ እንደ ተነሳ፣ እንዳረገ እየሆነ ነበር። አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም። አንተም የብዙዎች አባት ነህና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን።" አለው።
"እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ
ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ
ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል።
ዕረፍት
አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ
መዛሙርትን አፈራ። ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተጨዋወተ ዘለቀ። በተጋድሎ ሕይወቱም ከአሥር ጊዜ በላይ ሙቶ ተነስቷል። ሲያርፍም ገዳሙ በመላእክት ተሞላ።
ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ። አቅም ቢያጣ 'አምላከ አቢብ ማረኝ።' ብሎ ሦስት ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን በስምህ እንኳ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ።" ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ፤ በሰማይም ዕልልታ ተደረገ።
<3 ሰማዕታተ ፋርስ <3
ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው። ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል። ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው።
ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል። የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው።
"አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ።
ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው።
እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ!
በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ። ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም።
እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ።" ብሎናልና።
(ማቴ. ፭፥፵፬)
ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል።
በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል። የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና።
ፋርስ (Persia) በአሁን መጠሪያዋ 'ኢራን' የምትባል በቀደመው ዘመን የበርካታ እውነተኛ ክርስቲያኖች ቤት ነበረች። ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድን የመሰሉ አእላፍ ሰማዕታት በዚህች ሃገር ውስጥ በሁለተኛውና ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሰማዕትነት ጽዋዕን ጠጥተዋል። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመንም አባ ማሩና በተባለ ጻድቅ ሰው በዚህች ቀን ዐፅማቸው ተሰብስቦ ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል።
አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን። በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን።
እንኳን ለጻድቁ አቡነ ክፍለ ማርያም እና ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አቡነ ክፍለ ማርያም <3
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ክፍለ ማርያም በሐዋርያዊ አገልግሎቱ የተመሠከረለት፣
ለበርካታ ዓመታት በጾምና በጸሎት በአቱን አጽንቶ የኖረ፣
ከቅድስናው የተነሳ መላእክት ሰማያዊ ኅብስት ይመግቡት ውኃም ከአለት ላይ ይፈልቅለት የነበረ አባት ነው።
በዘመኑም ረሃብ ነበርና እርሷ ሳታውቀው እናቱን በረሃብ ጠውልጋ ቢያያት በጣም በማዘኑ እንዲባርከው ከቀረበለት የሰንበት ቁርስ ለእናቱ አድልቶ ብዙ ሰጣት። በዚህ ምክንያት መልአኩም ሰማያዊ ኅብስቱን አስቀረበት፤ ምንጩም ደረቀች።
ጥፋቱ የገባው አባ ክፍለ ማርያም ለአሥራ አንድ ዓመታት ንስሐ ገብቶ እግዚአብሔር መልሶለታል። ከብዙ የገድል ዓመታት በኋላም በዚህች ቀን ተሠውሯል።
<3 ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት <3
ይህን ቅዱስ "ፊልሞን መዓንዝር" ብሎ መጥራቱ የተለመደ ነው። እርሱ በቀደመ ሕይወቱ አዝማሪ (ዘፋኝ) ነበርና። ዘፋኝነት (አዝማሪነት) ደግሞ በክርስትና ከተከለከሉ ተግባራት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ዘፈን (ሙዚቃ) መስማትም ሆነ ማዳመጥ ኃጢአት ነው።
ነገር ግን ሁሉ እንዲድን የሚፈቅድ ጌታችን ጥሪውን ወደ ሁሉም ሰው በየጊዜው ይልካል። ቅዱስ ፊልሞንም የክርስቶስ ጥሪ የደረሰው በከንቱ የዘፋኝነት (የአዝማሪነት) ኑሮ ውስጥ ሳለ ነው።
ነገሩ እንዲህ ነው፦
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ (በ፪፻፺ዎቹ) አርያኖስ የሚባል ሹም በግብጽ (እንዴናው) ክርስቲያኖችን ጨፈጨፈ። ባለማወቅም ክርስቶስን የሚያመልኩ ሚሊየኖችን በሰይፍ በላቸው። ከዚህ ድርጊቱ መልስ ደግሞ በጣዖቱ (አጵሎን) ፊት እያስዘፈነ ከንቱነትን ይሰዋ ይዝናናም ነበር።
ከዘፋኞቹ መካከል ደግሞ ይህ ፊልሞን አንዱ ሆኖ ለዘመናት በፊቱ ተጫወተለት። አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ። አስቃሎን የሚባል ቅዱስ ክርስቲያን ለጣዖት እንዲሰዋ ታዘዘ።
ይህ አስቃሎን (አብላንዮስም ይባላል።) ወንድሙን ፊልሞንን ያድነው ዘንድ ተጠበበ። ወደ ፊልሞን ሒዶ "እኔ ገንዘብ እሰጥሃለሁ። የእኔን ልብስ ለብሰህ እኔን መስለህ ለጣዖት ሰዋልኝ።" አለው። አስቃሎን ይህንን ያለው ለጥበቡ ሲሆን ፊልሞን ግን "ገንዘብ ካገኘሁ" ብሎ የባልንጀራውን ልብስ ተሸፋፍኖ ወደ ጣዖቱ ፊት ቀረበ።
ያን ጊዜ ተሸፍኖ መስዋዕት ማቅረብ ክልክል ነውና ሹሙ አርያኖስ ግለጡት ሲል አዘዘ። ቢገልጡት ፊልሞን ሁኖ ተገኘ። መኮንኑ ገርሞት "ምን እያደረክ ነው?" ቢለው "እኔ ክርስቲያን ነኝ።" ሲል አሰምቶ ተናገረ።
ለጊዜው ሁሉም እየቀለደ መስሏቸው ነበር። ፊልሞን ግን ይህንን ያለው ከልቡ ነው። ምክንያቱም በቅዱስ አስቃሎን ልብስ ተመስሎ መንፈስ ቅዱስ ልቡን ለውጦለት ነበር። ተገልጦ ቀና ሲልም ቅዱሳን መላእክት ከበውት አይቶ ልቡ ጸንቶለታል።
ሹሙ አርያኖስም የቀልዱን እንዳልሆነ ሲያውቅ "ታብዳለህ?" ቢለው ፊልሞን "ምን አብዳለሁ! ዛሬ ገና ከእብደቴ ሁሉ ዳንሁ እንጂ።" ሲል መልሶለታል። አሕዛብ ሁሉ እያዩም በዚያች ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል ወርዶ አጥምቆታል።
በሆነው ሁሉ የተበሳጨው ሹሙም ቅዱስ ፊልሞንን ከክርስቶስ ፍቅር ይለየው ዘንድ ደበደበው፣ ገረፈው፣ ጥርሱን አረገፈው፣ ደሙንም መሬት ላይ አፈሰሰው። በዚህ ሁሉ ግን ጸና። ቅዱስ አስቃሎንም ፈጥኖ መጥቶ በመከራው መሰለው።
በመጨረሻም ሁለቱም ቅዱሳን በቀስት ተነድፈው ይገደሉ ዘንድ ተፈረደባቸው። ነገር ግን ለእነርሱ የተወረወረ ቀስት መንገዱን ስቶ የሹሙን (የአርያኖስን) ዓይን በማጥፋቱ ወታደሮቹ በንዴት ሁለቱንም ሰይፈው ገድለዋቸዋል።
ዓይኑ የጠፋበት አርያኖስም ስቃዩ ሲበዛበትና ከሚያመልካቸው የረከሱ ጣዖታት መፍትሔ ሲያጣ ከቅዱሳኑ ደም ተቀባ። ዓይኑም ፈጥኖ በራለት። በዚህም ምክንያት ምድራዊ ሹመቱን፣ ሃብት ንብረቱን፣ ትዳርና ቤቱን፣ ጣዖት አምልኮውን ትቶ በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት በቅቷል።
አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ አማላጅነት የምናስተውልበትን አዕምሮ አይንሳን። በረከታቸውንም ያድለን።
የካቲት ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ክፍለ ማርያም ዘዲባጋ
፪.ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት
፫.ቅዱስ አስቃሎን አናጉንስጢስ (ሰማዕት)
፬.አቡነ ገብረ መርዐዊ ዘአግዶ (ኢትዮጵያዊ)
፭.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት (የታላቁ ሐዋርያዊ ቅዱስ አትናቴዎስ ደቀ መዝሙር)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፫.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፬.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ
፭.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፮.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
"ስትጦሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ።.....
አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ፤ ፊትህንም ታጠብ። በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ያስረክብሃል።"
(ማቴ ፮፥፲፮-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ <3
ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል ትልቅ ሞገስ የነበረውና "የጌታችን ወንድም" ተብሎ የተጠራ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ የሞተችው እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች። በቤት ውስጥም ስምዖን፣ ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ የምትባል እኅትም ነበረችው።
እናቱ ማርያም ከሞተች በኋላ ዕጓለ ማውታ (ድሃ አደግ) ሆኖ ነበር። ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ ቤተሰብ ተቀየረ። የበረከት፣ የምሕረትና የሰላም እመቤት የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው።
እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ አለቀሰች። የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው ቆሽሸው ነበር። በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ ያሳዝን ነበር። እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም። ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውኃ አምጥታ የሕፃኑን ገላ አጠበችው። (በአምላክ እናት የታጠበ ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል።)
እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ከተወለደ በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ሕፃኑን ያዕቆብን ተንከባከበችው። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ግን ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ። ከስደት መልስ ግን ለሃያ አምስት ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ ትዝ ብላው አታውቅም። አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና።
ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና ወተትን) ብቻ ነው። ስለዚህም፦
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል መጽሐፍ።
(መልክዐ ስዕል)
ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል።
ለዚህም ምክንያቱ
፩.ለሠላሳ ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፣
፪.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእኅት ልጅ በመሆኑ፣
፫.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች በመሆናቸው፣
፬.ጌታችን ከትኅትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን "ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው። (ሥጋቸውን ተዋሕዶ ተገኝቷልና።)
ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ።" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ገልጧል።
(ያዕ. ፩፥፩)
ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው።
ከሰባ ሁለቱ አርድእት ተቆጠረ።
ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም።" ብሎ ማክፈልን አስተማረ።
መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ።
የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ አገለገለ።
በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ።
ሙታንን አስንስቶ፣ ድውያንን ፈውሶ፣ የመካኖችን ማኅጸን ከፍቶ፣ አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተአምራትን ሠራ። እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ መልካሙን ገድል ተጋደለ።
በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ ነው?" ሲሉ ጠየቁት። እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው፤ የእኔም ወንድሜ ነው።" እንዲላቸው ጠብቀው ነበር። (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት)
በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ። "ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦
አምላክ፣
ወልደ አምላክ፣
ወልደ አብ፣
ወልደ ማርያም፣
ሥግው ቃል፣ እግዚአብሔር ነው። እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት ወንድሙ አይደለሁም።" አላቸው።
ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት። በገድል የተቀጠቀጠ አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት። አንዱ ግን ከእንጨት የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ መታው። ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ። ሰማዕቱ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሐምሌ ፲፰ ቀን ሔደ።
ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር። በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ፣ ጸጉሩን ተላጭቶ፣ ገላውን ታጥቦና ልብሱን ቀይሮ አያውቅም።
"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ" እንዲል።
ከጾም፣ ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ አላራምድህ ብሎት ነበር። ስለዚህም አበው "ጻድቁ (ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል።
ቅዱሱ ሐዋርያ "የያዕቆብ መልእክት" የሚለውን ባለ አምስት ምዕራፍ መልእክት ጽፏል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን። በምልጃውም ምሕረትን ይላክልን።
የካቲት ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (የቅዱስ ዮሴፍ ልጅ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ)
፪.ቅዱስ አባ መላልዮስ ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት (በአንጾኪያ ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ በአርዮሳውያን ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት
፫.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
"የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት። ትዕግስትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።"
(ያዕ ፩፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
"አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት።"
(አባ ሕርያቆስ)
እንኳን ለቅድስት ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የኪዳን በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ሰባቱ ኪዳናት <3
"ተካየደ" ማለት "ተስማማ፣ ተማማለ" እንደ ማለት ሲሆን "ኪዳን" በቁሙ "ውል፣ ስምምነት" እንደ ማለት ነው። ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ሰዎችም ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል። ልዩነቱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው።
እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጓል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ ሰባት እንደ ሆኑ ታስተምራለች። ስለዚህም ዛሬ ፈጣሪ ቢረዳን እነዚህን ሰባት ኪዳናት በጥቂቱ እንመለከታለን።
"ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ - ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ።"
(መዝ. ፹፰፥፫)
፩. ኪዳነ አዳም
አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት፣ የፍጡራን አስተዳዳሪ፣ ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ ነው። እግዚአብሔር ከአዳም ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው። ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ።
(ዘፍ. ፫፥፩)
አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን ተስፋ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ኪዳንን ተቀበሉ።
(ቀሌምንጦስ፣ ገላ. ፬፥፬)
፪. ኪዳነ ኖኅ
ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት አሥር ትውልድ ዓለም በዓመፃ ተሞላች። ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች። ከመርከቡ ከወጣ በኋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት ቃል ኪዳን ተጋቡ። "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ" እንዲል።
(ዘፍ. ፱፥፲፪)
፫. ኪዳነ መልከ ጼዴቅ
መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ የክርስቶስም ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው። በአሥራ አምስት ዓመቱ መንኖ አጽመ አዳምን ይዞ በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት ነበር።
እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን አትሞታል። በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን አልቀመሰም። ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል።
(ዘፍ. ፲፬፥፲፯፣ ዕብ. ፯፥፩)
፬. ኪዳነ አብርሃም
ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት፣ ሥርወ ሃይማኖት፣ የጽድቅም አበጋዝ ነው። ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና እግዚአብሔር "በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ።" አለው።
(ዘፍ. ፲፪፥፩)
የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን ሰጠው።
(ዘፍ. ፲፯፥፩-፬)
፭. ኪዳነ ሙሴ
ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ፣ የእሥራኤል እረኛ፣ የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነው። በፈጣሪው ትዕዛዝ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለአርባ ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል።
(ዘጸ. ፳፥፩፣ ፴፩፥፲፰)
፮. ኪዳነ ዳዊት
ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት፣ ጻድቅ፣ የዋህና ቡሩክ የሆነ አባት ነው። እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ።" ሲል ምሎለታል።
(መዝ. ፻፴፩፥፲፩)
አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ "አልዋሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን።
(መዝ. ፹፰፥፴፭)
፯. ኪዳነ ምሕረት
በብሉይ ኪዳን የነበሩ ስድስቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲኦል ማዳን ግን አልቻሉም። ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ ነበር። ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ።
በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ፣ አድጎ፣ ተጠምቆ፣ አስተምሮ፣ ሙቶ፣ ተነስቶና ዐርጐ ሥጋ ማርያምን በዘባነ ኪሩብ አስቀመጠው። ኪዳነ ምሕረት (የምሕረት ኪዳን) የምንለው አንዱ ታዲያ ይሔው ነው።
የጌታችን መጸነሱ፣ መወለዱ፣ መሰደዱ፣ መጠመቁ፣ ማስተማሩ፣ ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ፣ መሰቀሉ፣ መሞቱና መነሳቱ፣ ማረጉና መንፈስ ቅዱስን መላኩ በአንድ ላይ ኪዳነ ምሕረት ይባላል። ታዲያ ይህ ሁሉ የተደረገው በሥጋ ማርያም ነውና የኪዳኑ ባለቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።
የእርሷ ኪዳን የስድስቱን አበው ኪዳናት ፍጹም በማድረጉ "የኪዳናት ማሕተም" ይባላል። የድንግል ማርያም ኪዳኗ ከሲኦልና ከገሃነም ሊታደገን አቅሙ አለውና። መድኃኒታችን ክርስቶስ ለድንግል እናቱ ቃል ኪዳኑን ያጸናላት ደግሞ ካረገ ከዓመታት በኋላ ጐልጐታ ላይ ነው።
እመ ብርሃን በዚያ ቁማ ስለ ኃጥአን ስታለቅስ "እናቴ ሆይ! በስምሽ ያመነውን በቃል ኪዳንሽ የተማጸነውን እምርልሻለሁ።" ብሎ ደስ አሰኝቷታልና። ይሔው በእመ ብርሃን ምልጃና ቃል ኪዳን ምዕመናን ከመቅሰፍትና ከገሃነመ እሳት ማምለጥ ከጀመሩ ሁለት ሺህ ዓመታት ሆኑ። ዛሬም እኛ ኃጥአን ልጆቿ ከእሳት እንደምታድነን አምነን በጥላዋ ሥር እንኖራለን።
"ኢትዝክሪ ብነ አበሳነ ኃጢአተነ ወጌጋየነ ማርያም እሙ ለእግዚእነ
በኪዳንኪ ወበስደትኪ ድንግል ተማሕጸነ።"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአታችን፣ አበሳችንና በደላችንን አታስቢብን ዘንድ በስደትሽና በኪዳንሽ ተማጽነናል።"
የአርያም ንግሥት፣ የሰማያውያንና ምድራውያን ሁሉ እመቤት፣ የአምላክ እናት፣ ቅድስት፣ ስብሕት፣ ክብርት፣ ልዕልት፣ ቡርክት፣ ፍስሕትና ጥዕምት የሆነች ድንግል ማርያም የድኅነታችን መሠረት ላመኑባት አንገት የማታስደፋ እውነተኛ አማላጅ ናት።
በዚህች ዕለት የካቲት ፲፮ ስለ ወገኖቿ የሰው ልጆች ፍቅር በእንባ ያቀረበችውን ልመና የባሕርይ አምላክ የሆነ ልጇ ተቀብሎ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላታል። በስምሽ ያመነ በቃል ኪዳንሽ የተማመነ እሳትን አያይም ብሏታል።
እንኳን ለታላቁ ሊቅና የተዋሕዶ ጠበቃ ቅዱስ ሳዊሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ <3
ቅዱስ ሳዊሮስ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው። ወቅቱ መለካውያን (ሁለት ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው። ሊቃውንት አንበሳ ሲሉ ይጠሩታል።
ቅዱሱ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ብዙ ሆኖላታል። የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል። ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ።
ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ።" አለችው። እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም።" ሲል መለሰላት። አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት።
እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ። መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው። ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጓዘ። እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ።
በምድረ ግብጽም የጵጵስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ፤ አጸና። በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ።
አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት። ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የካቲት ፲፬ ቀን ዐርፏል።
አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት የድንግል እመቤታችንን ጣዕሟን ፍቅሯን ያሳድርብን። የአበውን ሃብትና በረከትም አይንሳን።
የካቲት ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፪.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት
፫.አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳሳት
፬.ቅዱስ ዳርዮስ
፭.ቅድስት ሊድና
ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯.እናታችን ቅድስት ነሣሒት
"ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።"
(ይሁዳ ፩፥፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለኢትዮጵያውያን ሰማዕታት እና ቅዱስ ሶምሶን ረዓይታዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት <3
በ፲፱፻፳፱ ዓ.ም የካቲት ፲፪ ቀን ከሠላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት በሮማዊው የፋሽስት ጦር ደማቸው ፈሷል። እነዚህ ወገኖቻችን ደማቸው እንደ ጐርፍ አዲስ አበባ ላይ የፈሰሰው ስለ ሃገር ፍቅር ብቻ አልነበረም። ስለ ቀናች ሃይማኖት ተዋሕዶ ጭምር ነው እንጂ።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ግጻዌ ላይ ስማቸውን ጽፋ በቅዱስ ዳዊት መዝሙር እንዲህ ታስባቸዋለች።
"አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ። የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ። ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት።
የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች አደረጉ። የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት።
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ። የሚቀብራቸውም አጡ።"
(መዝ. ፸፰፥፩-፫)
ሰማዕታቱን እናስባቸው!
<3 ሶምሶን ረዓይታዊ <3
እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው። አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ነቢይና ካህን አድርጐ ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው።
አባታችን አዳም ግን ስህተት አግኝቶት ከገነት ወጣ። መከራና ፍዳም አገኘው። በኋላም ለመቶ ዓመታት አልቅሶ ንስሐ ገባ። ጌታም ንስሐውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው።
ስለዚህም ምክንያት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ትንቢት ሲነገር፣ ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር፣ ምሳሌም ሲመሰል ኖረ። ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ።
ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ። በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም። ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ።
ከእርሱም ይስሐቅ ከዚያም ያዕቆብ ደጋጉ ተገኙ። ያዕቆብም "እስራኤል" ተብሎ በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ። በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ረሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው።
በዚያም ለሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ። እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እስራኤልን አሰባቸው። የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው።
ይኸውም በጸናች እጅ በበረታችም ክንድ፣ በዘጠኝ መቅሰፍት፣ በአሥረኛ ሞተ በኩር፣ በአሥራ አንደኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው። በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው። ከዚህ ዘመን ጀምሮም እስራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ።
አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና አሮን በክህነት መሯቸው። ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ በአሮን አልዓዛር ተተኩ። እንዲህ እንዲህ እያለም ከኃያል ሰው ሶምሶን ረዓይታዊ ደረሱ። ይኸውም ከዓለም ፍጥረት አራት ሺህ ሁለት መቶ ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው።
በጊዜው እስራኤል ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሔርን ስላሳዘኑት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። የአካባቢው መንግሥታት እነ አሞን፣ አማሌቅና ኢሎፍሊ ስንኳ ያኔ ዛሬም ቢሆን እንደምትመለከቱት ዶሮና ጥሬ ናቸው።
በጊዜውም የእስራኤል ኃጢአት ስለ በዛ ኢሎፍላውያን (ፍልስጤማውያን) አርባ ዓመት በባርነት ገዟቸው። ንስሐ ሲገቡ ደግሞ ልጅ በማጣት ያዘኑ ማኑሄ እና ሚስቱ (እንትኩይ) በቅዱስ ሚካኤል ተበሥረው ኃያሉን ሶምሶንን ወለዱላቸው።
እርሱም ናዝራዊ (ከእናቱ ማኅጸን ለጌታ የተለየ) ነበርና ፍልስጤማውያንን ቀጥቶ ወገኖቹን እስራኤልን ከባርነት በአምላኩ ኃይል ታደገ።
ከኃይሉ ብዛት የተነሳም አንበሳን እንደ ጠቦት ይገድላል።
(መሳ. ፲፬፥፭)
ሦስት መቶ ቀበሮዎችን አባሮ ይይዛል።
(መሳ. ፲፭፥፫)
በብርቱ ገመዶች ሲያስሩት እንደ ፈትል ይበጣጥሰዋል።
(መሳ. ፲፭፥፲፬)
በአህያ መንጋጋ ሺህ ሰው ይገድላል።
(መሳ. ፲፭፥፲፭)
ጠባቂዎችን ከነ መቃናቸው ተሸክሞ ይወረውር ነበር።
(መሳ. ፲፮፥፫)
ውኃ ሲጠማውም ከአህያ መንጋጋ ላይ ፈልቆለት ጠጥቷል።
(መሳ. ፲፭፥፲፰)
በፍጻሜው ግን ደሊላ በምትባል ሴት ተታልሎ ምሥጢሩን በመግለጡና ጸጉሩ በመላጨቱ ኃይሉን አጥቷል። ጠላቶቹም ዓይኑን አውጥተው መዘባበቻ አድርገውታል።
በፍጻሜው ግን ኃይሉ እንዲመለስለት ፈጣሪውን ለምኖ አሕዛብ ለጣኦት በዓል እንደተሰበሰቡ የአዳራሹን ምሰሶ አፍርሶ አጥፍቷቸው ዐርፏል። (መሳ. ፲፫ - ፲፮)
ቅዱስ ሶምሶን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ (ምሳሌ) ነው።
በዘመኑ ሁሉ ቅዱስ ሚካኤል ረድቶታልና በዚህች ቀን መታሠቢያው ይደረግለታል።
አምላከ አበው ቅዱሳን መዓዛ ቅድስናቸውን ያሳድርብን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።
የካቲት ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ሠላሳ ሺህ ሰማዕታተ ኢትዮጵያ (ሮማዊው ፋሽስት የገደላቸው)
፪.ቅዱስ ሶምሶን ረዓይታዊ (የእስራኤል መስፍን)
፫.ቅዱስ አባ ገላስዮስ ገዳማዊ
፬.ቅድስት ዶርቃስ
፭.አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ድሜጥሮስ
፬.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፮.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፯.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
፰.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ
"ሶምሶንም 'ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ አስበኝ? አምላክ ሆይ!..... እባክህ አበርታኝ?' ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ።
.....ሶምሶንም 'ከፍልስጤማውያን ጋር ልሙት።' አለ። ተጐንብሶም ምሰሶዎችን በሙሉ ኃይሉ ገፋ።
.....በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ።"
(መሳ ፲፮፥፳፰-፴)
"እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ፣ ስለ ሶምሶንም፣ ስለ ዮፍታሔም፣ ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም፣ ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ። ጽድቅንም አደረጉ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፪-፴፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር