gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ቅዱስ ገብርኤል መልአከ ፍሥሓ በእሳት ሥዑል
ሰበካ ለድንግል ምጽአቶ ለቃል
ወርቀ ወሜላተ እንዘ ትፈትል"

(በእሳት የተቀረጸ የደስታ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወርቅንና ሐርን ስትፈትል የቃል መምጣቱን (ሥጋ መሆኑን) ለድንግል አበሠራት።)
(ቅዱስ ያሬድ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ክርስቲያናዊ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ <3

ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያህል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም። ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒና ከአረማዊ አባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ።

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ ጊዜ) ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር። ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በተደረገው የአርባ ዓመታት ዘመቻ አብያተ መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ። ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ። ሚሊየኖች በግፍ አለቁ።

የዚያን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም። ምክንያቱም ያን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ ቀርነ ሃይማኖት የቆመው ብዙ ሥርዓት የተሠራው ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና።

ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት፣ ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል። በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል። "ቆስጠንጢኖስ" ማለት "ሐመልማል" ማለት ነው።

ዳግመኛ በዚህች ቀን የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በሆነው ሞቱ በመቃብር ውስጥ አድሯል።

ጌትነት ያለው አምላካችን በይቅርታው ይጐብኘን። መልካም መሪንም ይስጠን።

መጋቢት ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (ጻድቅ ንጉሥ)
፪.ቅድስት እሌኒ ንግሥት

ወርኀዊ በዓላት
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

"እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።"
(፩ጢሞ ፪፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

መጋቢት ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ (ፍቁረ እግዚእ)
፪.ቅዱሳት አንስት (ከእግረ መስቀሉ ያልተለዩ)
፫.አምስት መቶ ቅዱሳን ባልንጀሮች (በጌታ ስቅለት ጊዜ ከሞት የተነሱ)
፬.ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
፭.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት አለቃ)
፮.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት (የኢትዮጵያ ንጉሥ)
፯.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ መብዐ ጽዮን ጻድቅ
፪.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
፫.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፬.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

"የተጠራችሁለት ለዚህ ነው። ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም። ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም። ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራንም ሲቀበል አልዛተም።
.....እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።"
(፩ጴጥ ፪፥፳፩-፳፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጥንተ በዓለ ምሴተ ሐሙስ እና ኢዮጰራቅስያ ድንግል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ምሴተ ሐሙስ <3

ስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ምሴተ ሐሙስ" በምትባለው በዚህች ዕለት፦
፩.በወዳጁ በአልዓዛር ቤት የዓለማት ፈጣሪ ሲሆን በትሕትና ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል።
፪.ለእኛ ድኅነት ይሆነን ዘንድ ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቷል።
፫.በጌቴሴማኒ ላበቱ እንደ ደም እየተንጠፈጠፈ ጸልዮ "ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ።" ሲል አስተምሯል።
፪.ምሽት ሦስት ሰዓት አካባቢ ይሁዳ ሊቃነ ካህናቱን አስከትሎ መጥቶ ለሠላሳ ብር አሳልፎ ሰጥቶታል።
(ማቴ. ፳፮፥፳፮ ፣ ዮሐ. ፲፫፥፩)

ይህ ሁሉ ለእኛ ድኅነት ተፈጽሟልና ምስጋናና ክብር ለፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን።

<3 ኢዮጰራቅስያ ድንግል <3

ዳግመኛ በዚህ ዕለት እናታችን ቅድስት ኢዮጰራቅስያ ድንግል አርፋለች።

ቅድስቲቱ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረች እናት ስትሆን ገና በዘጠኝ ዓመቷ ምድራዊ ሃብትን ንቃ መንናለች። ምክንያቱም ዘመዶቿ የሮም ነገሥታት እነ አኖሬዎስ ነበሩና። ድንግል ኢዮጰራቅስያ በገዳም፣ በጾምና በጸሎት፣ በፍፁም ትሕትናና ታዛዥነት እንዲሁም በፍቅር ኑራ በዚህች ቀን ዐርፋለች።

ከቅድስት እናታችን በረከት አምላኳ ይክፈለን።

መጋቢት ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ሐዋርያት
፪.ቅድስት ድንግል ኢዮጰራቅስያ
፫.ቅዱስ ፍርፍርዮስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል። እኔም በርሱ እኖራለሁ።"
(ዮሐ ፮፥፶፬-፶፮)

"እግራቸውን አጥቦ ልብሱንም አንስቶ ዳግመኛ ተቀመጠ። እንዲህም አላቸው፦ 'ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ። እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባል።' "
(ዮሐ ፲፫፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓለ ጽንሰት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ <3

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዓይን ናቸው። ጻድቁን መንካት የቤተ ክርስቲያንን ዓይኗን መጠንቆል ነው።

ተክለ ሃይማኖት እንደ ሊቃውንት ሊቅ፣ እንደ ሐዋርያት ሰባኬ ወንጌል፣ እንደ ሰማዕታት ብዙ ግፍ የተቀበሉ፣ እንደ ጻድቃን ትሩፋት የበዛላቸው፣ እንደ ደናግል ንጽሕናን ያዘወተሩ፣ እንደ ባሕታውያን ግኁስ፣ እንደ መላእክትም ባለ ክንፍ አባት ናቸው። ለዚህ ነው ተክለ ሃይማኖትን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዓይኔ የምትላቸው።

<3 ልደት <3
መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው። እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ፣ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል።

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል። በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል።

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ ቀን በ፲፪፻፮ ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን በ፲፪፻፯ ዓ/ም ነው። በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል። ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል።

<3 ዕድገት <3
የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል። ይህንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል። በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት፣ ሐዲሳትን) ተምረዋል። በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል። ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል።

<3 መጠራት <3
አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ።

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ። "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን። ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ። ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በግርማ ዐረገ። ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም። ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ።

<3 አገልግሎት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ። በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ሁለት መልክ ነበራት።
፩ኛ.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል።
፪ኛው. ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር።

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ። ሕዝቡንና መሳፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል።

<3 ገዳማዊ ሕይወት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል። እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በሦስት ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል።

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለአሥራ ሁለት ዓመታት፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለሰባት ዓመታት፣ በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለሰባት ዓመታት በአጠቃላይ ለሃያ ስድስት ዓመታት አገልግለዋል።

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለሃያ ሁለት ዓመታት ቆመው ጸልየዋል። በተሰበረ እግራቸውም ስድስት ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለሰባት ዓመታት ጸልየዋል።

<3 ስድስት ክንፍ <3
ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል። ጻድቁ ምድረ እስራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ፣ እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር።

የወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው። ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር።

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም። በገሃድ፦
በቤተ መቅደስ ብስራቱን፣
በቤተ ልሔም ልደቱን፣
በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣
በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣
በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር።

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ።
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አባታችንን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው።

በዚያም፦
የብርሃን ዓይን ተቀብለው፣
ስድስት ክንፍ አብቅለው፣
የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣
ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣
ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው፣
ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል።

<3 ተአምራት <3
የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው።
ሙት አንስተዋል፣
ድውያንን ፈውሰዋል፣
አጋንንትን አሳደዋል፣
እሳትን ጨብጠዋል፣
በክንፍ በረዋል፣
ደመናን ዙፋን አድርገዋል።

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል። በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል። በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና።

<3 ዕረፍት <3
ጻድቅ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው፣ መከራን በብዙ ተቀብለው፣ እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ ቀን በ፲፫፻፮ ዓ/ም ዐርፈዋል። ጌታ፣ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል። አሥር ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል።

አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ አባታችን በረከትን ይክፈለን።

መጋቢት ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት (ጽንሰታቸው)
፪.ቅዱሳን እግዚእ ኃረያና ጸጋ ዘአብ
፫.ቅዱስ አባ መቃርስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አጋቢጦስ ጻድቅ
፪.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፫.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
፬.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮.ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ

"በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው። የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው። የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል።"
(ምሳሌ ፲፥፮-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ዳንኤል ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዳንኤል <3

ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፣ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ።

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)
ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ።

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል።
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ።
(ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው። እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል።

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ። እናንተ በድካማቸው ገባችሁ።" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል።
(ዮሐ. ፬፥፴፮)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፤ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ።" እንዳለ ጌታ በወንጌል።
(ማቴ. ፲፫፥፲፮ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ።

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት፣ አራቱ ዐበይት ነቢያት፣ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ።

አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት፦
ቅዱስ አዳም አባታችን
ሴት
ሔኖስ
ቃይናን
መላልኤል
ያሬድ
ኄኖክ
ማቱሳላ
ላሜሕ
ኖኅ
አብርሃም
ይስሐቅ
ያዕቆብ
ሙሴና
ሳሙኤል ናቸው።

አራቱ ዐበይት ነቢያት፦
ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
ቅዱስ ኤርምያስ
ቅዱስ ሕዝቅኤልና
ቅዱስ ዳንኤል ናቸው።

አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት፦
ቅዱስ ሆሴዕ
አሞጽ
ሚክያስ
ዮናስ
ናሆም
አብድዩ
ሶፎንያስ
ሐጌ
ኢዩኤል
ዕንባቆም
ዘካርያስና
ሚልክያስ ናቸው።

ካልአን ነቢያት ደግሞ፦
እነ ኢያሱ
ሶምሶን
ዮፍታሔ
ጌዴዎን
ዳዊት
ሰሎሞን
ኤልያስና
ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው።

ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ።
የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እስራኤል)ና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ።

በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦
ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)፣
ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)፣
ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ።
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ።

ዳንኤል ማለት እግዚአብሔር ፈራጅ ነው ማለት ነው።
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስድስት መቶ ዓመታት አካባቢ ከይሁዳ ነገሥታት ዘር ተወለደ። ገና በሕፃንነቱ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ማርኮ ወደ ባቢሎን ሲያወርዳቸው አብሮ ወርዷል።

ከሕፃንነቱ ጀምሮ በአምላኩ ፍቅር ታሥሮ ከሦስቱ ጓደኞቹ (አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል) ጋር ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር። በዘመኑ እንደርሱ ያለ መተርጉመ ሕልም አልተገኘምና ለወገኖቹ ሞገሳቸው ነበር።

ኃይለኛውን ንጉሥ ናቡከደነጾርን ጨምሮ የባቢሎንና ፋርስ ነገሥታት ያከብሩት ይወዱትም ነበር።

ቅዱስ ዳንኤል በጥበብና በሃይማኖት የአሕዛብን አማልክት ድል ነስቷል። አሕዛብ በተንኮል ወደ አናብስት ጉድጓድ ውስጥ ቢያስጥሉት እግዚአብሔር የአናብስቱን አፍ ዘግቷል። ዕንባቆምንም አምጥቶ መግቦታል።

ቅዱስ ዳንኤል የብሉይ ኪዳኑ "አቡቀለምሲስ" ይባላል። ስለ ጌታችን የማዳን ሥራና ስለ ዳግም ምጽዐቱ በግልጥ ተናግሯል። ሐረገ ትንቢቱም አሥራ ሁለት ምዕራፍ ነው። የዘመኑ አይሁድ ክርስቶስ ገና አልተወለደም ለማለት ዳንኤልን ጠልተውታል።

ታላቁ ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ዳንኤል እስራኤል ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ አብሯቸው አልመጣም። ከሰባ ዓመታት በላይ በጸጋ ትንቢት ኑሮ እዚያው ባቢሎን ውስጥ አርፏል።

ፈጣሪ ከበረከቱ ለሁላችን ያድለን።

ዳግመኛ በዚህች ቀን ክፉዎች አይሁድ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገድሉት ዘንድ በቤተ ቀያፋ መከሩ።

እርሱ ቸሩ አምላክ ከክፉ መካሪዎች ይሠውረን።

መጋቢት ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል
፪.አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ (ፍልሰታቸው)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
፬.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭.አባ ሳሙኤል
፮.አባ ስምዖን
፯.አባ ገብርኤል

"የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ። ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጉድጓድ ጣሉት።.....
ድንጋይም አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙት።.....
በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሳ።..... ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው።..... ዳንኤልም ንጉሡን..... በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና..... አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ። አንዳችም አልጐዱኝም አለው።.....
ዳንኤልም ከጉድጓድ ወጣ። በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።"
(ዳን ፮፥፲፮-፳፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ በዓልና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወርኀዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሱ ቤተሰብ እና ጌታ <3

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና የዓለም ሁሉ ጌታ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ቀን ወደ ቢታንያ ሔዶ እነ ቅዱስ አልዓዛርና ቤተሰቦቹ እንግድነት ተቀብለውታል።

በዚያም ቅድስት ማርታ በጌታ ፊት ስታገለግል ቅዱስ አልዓዛር ከጌታ ጐን ተቀምጦ ቅድስት ማርያ በሦስት መቶ ዲናር የገዛችውን ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች። እግሩንም በጠጉሯ አበሰች።
(ዮሐ. ፲፪፥፩)

ለዚያ የተባረከ ቤተሰብም ታላቅ በረከት ሆነ። በእርግጥም ድንቅ ነው። ጌታን በቤት ማስተናገድ ፍፁም መታደል ነው።

ዳግመኛ በዚህች ቀን ይሁዳ በሦስት መቶ ዲናሩ ሽቱ አመካኝቶ በጌታ ላይ አንጎራጎረ። አይሁድ ደግሞ አልዓዛርን ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ። ምክንያቱም ጌታችን በእርሱ ላይ የሠራትን ድንቅ እያዩ ከአይሁድ ወገን ብዙዎቹ ያምኑ ነበርና።

ቤተ አልዓዛርን የባረከ ጌታ በቸርነቱ የእኛንም ይባርክልን።

መጋቢት ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሱ ቤተሰብ (አልዓዛር፣ ማርያና ማርታ)
፪.አባታችን ላሜኅ (የማቱሳላ ልጅ - የጻድቁ ኖኅ አባት)
፫.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም
፪.አበው ጎርጎርዮሳት
፫.አቡነ ምዕመነ ድንግል
፬.አቡነ አምደ ሥላሴ
፭.አባ አሮን ሶርያዊ
፮.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

"የወንድማማች መዋደድ ይኑር። እንግዶችን መቀበል አትርሱ። በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና። ከእነርሱ ጋር እንደታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ። የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ።"
(ዕብ ፲፫፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳኑ የአስከናፍር ቤተሰብ ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አስከናፍር <3

ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አስከናፍር የሚባል ደግ ክርስቲያን ማርታ የምትባል በሃይማኖትና ምግባር የምትመስለውን ሴት አግብቶ ይኖር ነበር። እንደ ሕጉና ሥርዓቱ በሥጋ ወደሙ ተወሥነው እንግዳ ቢቀበሉ ነዳያንን ቢያበሉ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ አርቃድዮስና ዮሐንስ የሚባሉ ልጆችን ሰጣቸው።

አስከናፍርና ማርታ ልጆቻቸውን ጥበብ መንፈሳዊን (ቃለ እግዚአብሔርን) አስቀድመው አስተምረው ሥጋዊ ጥበብን እዲማሩላቸው ቢልኳቸው መንገድ ላይ መርከብ ተሰብሮባቸው ብዙዎቹ ሲሞቱ ወንድማማቾች ግን የመርከብ ስባሪ ወደተለያየ ቦታ አድርሷቸዋል።

አርቃድዮስና ዮሐንስ "ወደ ዓለም አንመለስም።" ብለው መነኑ። ወላጆቻቸው የሆነውን ሰምተው በጭንቅ ሃዘንና ለቅሶ ለብዙ ጊዜ ኑረዋል። ከዘመናት በኋላ ግን የልጆቻቸውን መኖር በራእይ የተረዱት አስከናፍርና ማርታ ሃብት ንብረታቸውን ለነዳያን አካፍለው ወደ በርሃ መንነው ሔደዋል።

ጥበበኛ እግዚአብሔር አራቱንም አገናኝቷቸው ለብዙ ዓመታት በአንድ ገዳም ውስጥ ተጋድለዋል።
በዚህች ዕለትም አራቱም ወደ ሰማያዊው ሠርግ ተጠርተዋል።

ቸር አምላክ ከቅዱሱ ቤተሰብ በረከት ይክፈለን።

መጋቢት ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አስከናፍር፣ ሚስቱ ማርታ፣ ልጆቹ አርቃድዮስና ዮሐንስ
፪.ቅዱስ አርስጥቦሎስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት - የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር)
፫.ሰባቱ ቅዱሳን ሰማዕታት (ከተለያየ ቦታ ተሰብስበው በክርስቶስ ስም የሞቱ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፬.አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

"እንግዲህ ወንዶች በሥፍራ ሁሉ አለ ቁጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ። እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ። እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።"
(፩ጢሞ ፪፥፰-፲)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ አልዓዛር ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አልዓዛር ሐዋርያ <3

ቅዱስ አልዓዛር በሃገረ ቢታንያ ከእኅቶቹ ማርያና ማርታ ጋር ይኖር ነበር። ሦስቱም ድንግልናቸውን ጠብቅው ጌታችንን ያገለግሉት ነበርና አልዓዛርን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ማርያና ማርታን ደግሞ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል።

በወንጌል ጌታችን ይወዳቸው እንደነበር ተገልጧል።
(ዮሐ. ፲፩፥፫)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወድ የሚያበላልጥ ሆኖ አይደለም። ይልቁኑ በምሥጢር እነርሱ ተወዳጅ የሚያደርጋቸውን ሥራ ይሠሩ እንደነበር ሲነግረን ነው እንጂ።

ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን ጌታችን በነ አልዓዛር ቤት በእንግድነት ይስተናገድ ነበር።
(ዮሐ. ፲፪፥፩)
በመጨረሻዋ ምሴተ ሐሙስም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለሐዋርያቱ ያቀበላቸው በእነዚህ ቅዱሳን ቤት ውስጥ ነው።

ቅዱስ አልዓዛር በጽኑዕ ታሞ በዚህች ቀን ዐርፏል። ቅዱሳት እኅቶቹ ማርያና ማርታ ከታላቅ ለቅሶ ጋር ዕለቱኑ ቀብረውታል።
(ዮሐ .፲፩)

ቸር ጌታችን ክርስቶስ ከአራት ቀናት በኋላ ሊያስነሳው ይመጣልና ከበረከቱ ይክፈለን። (ይቆየን)

መጋቢት ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አልዓዛር ጻድቅ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ቴዎቅሪጦስ አናጉንስጢስ (ሰማዕት)
፫.ቅዱስ ተላስስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሴፍ ኤጲስ ቆጶስ
፭.ቅዱስ ጊዮርጊስ መስተጋድል

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
፫.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
፬.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፭.አባ ገሪማ ዘመደራ
፮.አባ ጰላሞን ፈላሢ
፯.አባ ለትጹን የዋህ

"ጌታ ኢየሱስም 'ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል። የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም። ይህን ታምኛለሽን?' አላት። እርስዋም (ማርታ) 'አዎን ጌታ ሆይ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ።' አለችው።"
(ዮሐ ፲፩፥፳፭-፳፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ ሰለፍኮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሰማዕቱ ሰለፍኮስ <3

ቅዱስ ሰለፍኮስ በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ክርስቲያን ወጣት ነው። በወቅቱ ያ የጭንቅና የመከራ ዘመን ከመምጣቱ በፊት በተቀደሰ ጋብቻ ለመኖር አስጠራጦኒቃ የምትባል ደግ የሆነች ክርስቲያናዊት ወጣት አጭቶ ነበር።

በዕጮኝነት ዘመናቸው ጾምን፣ ጸሎትንና ንጽሕናን በመምረጣቸው ያየ ሁሉ ያደንቃቸው ነበር።
ታዲያ የሠርጋቸው ቀን እየቀረበ ሲመጣ ያ የመከራ ዘመን (ዘመነ ሰማዕታት) ጀመረ።

ሁለቱ ንጹሐን ወጣት ክርስቲያኖች ተመካከሩና ወሰኑ። በምክራቸውም መሠረት ሁለቱም ከነ ድንግልናቸው ሰማዕትነትን ለመቀበል ተዘጋጁ። በዚህች ዕለትም ስለ ቀናች ሃይማኖትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ከብዙ ስቃይ በኋላ በከሃዲው ንጉሥ ትዕዛዝ ቅዱስ ሰለፍኮስ በሰማዕትነት አልፏል።

ከቅዱሱ ሰማዕት በረከት አምላከ ቅዱሳን ያድለን።

መጋቢት ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሰለፍኮስ ሰማዕት
፪.እናታችን ቅድስት ሣራ ጻድቅት (ግብጻዊት)
፫.አባ ሕልያስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ አፈ በረከት
፫.ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ
፬.ቅድስት እንባ መሪና
፭.ቅድስት ክርስጢና

"ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና። ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው። አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ። ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ። እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው። ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ።"
(፩ቆሮ ፯፥፯-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአርባ ሐራ ሰማይ ቅዱሳንና ለታላቁ ቅዱስ መቃርስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አርባ ሐራ ሰማይ <3

አርብዐ ሐራ ሰማይ ማለት በዘመነ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሰማዕትነትን የተቀበሉ አርባ ጭፍሮች ናቸው። "ሐራ ሰማይ" የተባሉት በምድር ሲሠሩት የቆዩትን የውትድርና ሥራ ትተው የክርስቶስ (የሰማያዊው ንጉሥ) ጭፍራ ለመሆን በመብቃቸው ነው።

አርባው ባልንጀሮች ወጣትና ጐበዝ ክርስቲያኖች ነበሩ። በእርግጥ እነርሱ ሰማዕትነት የተቀበሉበት ጊዜ ዘመነ ሰማዕታት አልነበረም። ነገር ግን ሰማዕትነት የጊዜ፣ የቦታ፣ የሁኔታ፣ የእድሜ፣ የጾታ፣ የዘር..... ልዩነት አያግደውምና እነዚህ ወጣቶች ለዚህ ክብር በቅተዋል።
ነገሩ እንደዚህ ነው፦
በ፫፻፴ዎቹ አካባቢ የዓለም ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አንዱን መኮንኑን ወደ ቂሣርያ አካባቢ ይልከዋል። የተላከው አካባቢውን ለማስተዳደር ሲሆን ቦታው ስብስጥያ (ሴባስቲ) ይሰኛል።

መኮንኑ ክርስቲያኖችን እንዲንከባከብ ጥብቅ ትዕዛዝ ከንጉሡ ቢሰጠውም ፍቅረ ጣዖት በልቡ የነበረበት ሰው ነውና ክርስቲያኖችን ይጨቁን፣ ያሰቃይ፣ ይገድል፣ አብያተ ክርስቲያናትን ያፈርስ ገባ።

በጊዜው ይህንን የተመለከቱት አርባው ጭፍሮች በአንድነት መክረው መኮንኑን ገሠጹት። ስመ ክርስቶስንም ሰበኩለት። እርሱም በፈንታው አርባውን አስሮ ብዙ አሰቃያቸው።

በመጨረሻ ግን አርባውንም የበረዶ ግግር አስቆፍሮ ከነ ሕይወታቸው እስከ አንገታቸው ቀብሮ ለሠላሳ ዘጠኝ ቀናት ያለ ምግብ በጽኑ ስቃይ አቆያቸው። በአርባኛው ቀን ግን ከአርባው አንዱ "ይህን ሁሉ መከራ የምቀበል ለምኔ ነው?" ብሎ "አውጡኝ!" እያለ ጮኸ።

ክርስቶስን አስክደው ወደ ውሽባ ቤት (ሻወር ቤት) ሲያስገቡት ፈጥኖ ሞተ። በነፍስም በሥጋም ተጐዳ። ነገር ግን ከአረማውያን ወታደሮች አንዱ "እኔን አስገቡኝ።" ስላለ እንደገና አርባ ሆኑ።

በዚህች ዕለትም አርባውን ጭን ጭናቸውን በመጅ እየሰበሩ ሲገድሏቸው ቅዱሳን መላእክት በአክሊል ከልለው በዝማሬ አጅበው ወደ ገነት ወስደዋቸዋል። ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም በጊዜው ነበርና ገድላቸውን ጽፎ ውዳሴ ደርሶላቸዋል። ቤተ ክርስቲያናቸውንም አንጾ የካቲት ፲፮ ቀን እንዲቀደስ አድርጓል።

ብጹዕ አባታችን አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ በቅዱሳኑ ላይ የሆነውን ነገርና ሥልጣነ እግዚአብሔርን እያደነቀ እንዲህ ሲል ተናግሯል።

"ኦ አውጻኢሁ ለዘእንተ ውስጥ
(በውስጥ ያለውን የምታስወጣ)"
"ወአባኢሁ ለዘእንተ አፍአ
(በውጪ ያለውንም የምታስገባ)"
"ወይእዜኒ ስማዕ አውያቶሙ ለሕዝብከ እለ ይጼውዑከ በጽድቅ።
(እንግዲህ በእውነት የሚጠሩህን የወገኖችህን ጩኸት /ልመና/ ስማ)"
(ቅዳሴ ማርያም ቁ.፻፵፮)

ስለዚህ በውስጥ ያለን አንታበይ። ያለንበት የእኛ አይደለምና። እንዳንወድቅም እንጠንቀቅ። ብዙዎቹ የቆሙ ሲመስላቸው ወድቀዋልና። ያሉ ሲመስላቸውም ወጥተዋልና።

በውጪ ያለንም ተስፋ አንቁረጥ። ወደ ኋላም አንበል። ወደ ቤቱ ሊመልሰን በክብሩ ማደሪያ ሊያኖረን የታመነ አምላክ አለንና።

ቸሩ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ገብቶ ከመውጣት አግኝቶ ከማጣት ይሠውረን። ከሰማዕታቱ በረከትም አይለየን።

<3 ታላቁ ቅዱስ መቃርስ <3

ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ፣ ከሰማንያ ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ፣ በግብጽ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ፣ ከሃምሳ ሺህ በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው።

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብጽ ወደ እስያ በርሃ ከጓደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል። በዚያ ለሁለት ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በኋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነ ንጉሳቸው አጥምቀዋል።

በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ አዕላፍ መላእክትን በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን፣ ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን፣ ማርቆስን፣ ጴጥሮስን፣ ጳውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል። በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።

ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከሁለት ዓመታት ስደትና መከራ በኋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልአኩ ኪሩብ በክንፉ ተሸክሞ ወደ ግብጽ መልሷቸዋል። በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከሃምሳ ሺህ በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል።

ከቅዱሳን አባቶቻችን የስደት በረከት ፈጣሪ አይለየን።

መጋቢት ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ - ስደቱ)
፪.ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ
፫.አርባ ቅዱሳን ሰማዕታት (ከሃገረ ስብስጥያ)
፬.ቅዱስ ዲዮናስዮስ (ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬.ቅዱስ አስከናፍር
፭.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ። ሐሴትንም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና።"
(ማቴ ፭፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ አቡነ አሌፍ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ አሌፍ <3

ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮጵያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት። አባ አሌፍ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው።

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው። በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር፦
፩.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ፣
፪.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግሥት)ና
፫.ገዳማዊ ሕይወት ነው።

አባ አሌፍን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግሥት ነው። እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል። አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል።

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ጰንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ። ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ።

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮጵያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም። ስለዚህም በ፬፻፸ዎቹ ዓ.ም አልዓሜዳ በኢትዮጵያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ።

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው። ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው። ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች።
አባ አሌፍና ስምንቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር።

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዚያው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ። በወቅቱ በአቡነ ሰላማ፣ በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ አሌፍ እንደ ገና አቀጣጠሉት።

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት። የካደውን እየመለሱ የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ።

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው። በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ አሌፍ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማኅበር ነበር። በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም።

የነ አባ አሌፍ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ። ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው። እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ።
ጰንጠሌዎን በጾማዕት፣
ገሪማ በመደራ፣
ሊቃኖስ በቆናጽል፣
አረጋዊ በዳሞ፣
ጽሕማ በጸድያ፣
አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ (እዚያው ትግራይ) ሆነ።
ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ።

አባ አሌፍ የተወለዱት አውሎግሶንና አትናስያ ከተባሉ ደጋግ ወላጆች ቂሳርያ ውስጥ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ጻድቁ በሕፃንነታቸው ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ገብተው ከዓመታት ተጋድሎ በኋላ ከስምንቱ ጓደኞቻቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ከተስዓቱ /ዘጠኙ/ ቅዱሳን አንዱ ናቸው።

በዐፄ አልዓሜዳ ዘመን አክሱም አካባቢ (ቤተ ቀጢን) የሃገራችንን ቋንቋ አጥንተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተርጉመዋል። ለሕዝቡም የወንጌልን የምሥራች ሠብከዋል።

ከዚያም ገዳም መሥርተው አምስት መቶ መነኮሳትን ሰብስበው ለሰባ ዓመታት በቅድስና ኑረዋል። ለዘጠኙ ቅዱሳን ሁሉ ስም ያወጡት የዘመኑ ሰዎች ቀድመው ወደ አክሱም ስለ ገቡ ጻድቁን "አሌፍ" ብለዋቸዋል። በዕብራይስጥኛ "አንደኛ" ማለት ነው። ጻድቁ ከፈጣሪያቸው የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብለው በዚህች ቀን ዐርፈዋል።

አምላከ አበው ቅዱሳን በምልጃቸው ይማረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

መጋቢት ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ አሌፍ ጻድቅ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)
፪.ቅዱስ ቴዎቄጤኖስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ባስሊዖስ (ጳጳስና ሰማዕት)
፬.አባ ኤፍሬም ሰማዕት
፭.አባ ኤልያስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፬.ብፁዐን ኢያቄምና ሐና
፭.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

"ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን?
..... የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?"
(፩ቆሮ ፮፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ዕፀ መስቀል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዕፀ መስቀል <3

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ በማኅጸነ ማርያም እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ፣ በኅቱም ድንግልና ተወልዶ፣ በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ፣ ከግራ ቁመት፣ ከገሃነመ እሳት፣ ከሰይጣን ባርነት፣ ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል።
"እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ" እንዳለ ሊቁ።

ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል። ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ ትዕምርተ መስቀል ናት።

እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት (ዘፍ. ፬፥፲፭) ጀምሮ ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት(ዘፍ. ፳፪፥፮)፣ ቅዱስ ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል (ዘፍ. ፳፰፥፲፪)፣ ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ(ዘፍ. ፵፰፥፲፬)፣ ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው የሙሴ በትር (ዘጸ. ፲፬፥፲፭)፣ የናሱ ዕባብ የተሰቀለበት እንጨትን (ዘኁ. ፳፩፥፰) ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል።

ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩህ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው።" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል።
(መዝ. ፶፱፥፬)

በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት። ደሙን አፈሰሰበት። ዓለምንም አዳነበት። ስለዚህም "መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል።

ቅዱስ ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል፤ መመኪያችን ነውና።
(፩ቆሮ. ፩፥፲፰ ፣ ገላ. ፮፥፲፬)

አንዳንዶቹ እኛን "የተሰቀለውን ትታችኋል።" ይሉናል። የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአማልክት አምላክ፣ ሁሉ በእጁ የተያዘ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና።

ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን። እናመሰግነዋለን፤ እናከብረዋለን። "ቤዛ፣ ጽንዕ፣ መድኃኒት፣ ኃይል" እያልንም እንጠራዋለን። አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል።

በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል። ጠላትንም አሳፍረዋል። እኛም በመስቀሉ አምነን ከብረን ገነን እንኖራለን። ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም።

<3 በዓለ መስቀል <3

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በኋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ። የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም።

መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት። አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ። ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ።

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ እናታችን ቅድስት ዕሌኒ (ሔለና) በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት፣ በቅዱስ ኪራኮስ መሪነት፣ በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች።

መስከረም ፲፯ ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት ፲ ቀን ተጠናቆ ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል፤ ሙታን ተነስተዋል። ከአሥር ዓመት በኋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም ፲፯ ቀን ተቀድሷል።

ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ አፄ ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ በጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ (ግሸን ማርያም) ተለብጦ ተቀምጧል።

አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን። ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን።

መጋቢት ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፪.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፫.ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ
፬.ቅዱስ መቃርስ ዘኢየሩሳሌም

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
፬.አቡነ መልክአ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)

"የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።
.....መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ። የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ። እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን።"
(፩ቆሮ ፩፥፲፰-፳፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ <3

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም። "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው፣ ልዑክ፣ የተላከ፣ የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው። በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፦
የፍጥረታት ሁሉ ጌታ የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ አድጐ፣ ተጠምቆ፣ ጾሞ ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር።

ከተከተሉት የአምስት ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት መረጠ።
እሊህም፦
፩.ጴጥሮስ የተባለ ስምኦን
፪.እንድርያስ (ወንድሙ)
፫.ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
፬.ዮሐንስ (ወንድሙ)
፭.ፊልጶስ
፮.በርተሎሜዎስ
፯.ቶማስ
፰.ማቴዎስ
፱.ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
፲.ታዴዎስ (ልብድዮስ)
፲፩.ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን)ና
፲፪.ማትያስ (በይሁዳ የተተካ) ናቸው።
(ማቴ. ፲፥፩)

እነዚህን አሥራ ሁለት አርድእቱን ከጠራ በኋላ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር። ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር።

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በኋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው። ለዓለም እረኞች የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ። እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው።
(ማቴ. ፲፥፲፮ ፣ ዮሐ. ፲፮፥፴፫)
በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው።
(ማቴ. ፲፱፥፳፰)

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ። "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።" (ማቴ. ፲፰፥፲፰)
"ይቅር ያላችኋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፤ ያላላችኋቸው ግን አይቀርላቸውም።"
(ዮሐ. ፳፥፳፫)

የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. ፲፮፥፲፱)፣ እረኝነትን (ዮሐ. ፳፩፥፲፭) ተቀበሉ። ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው፣ የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. ፭፥፲፫) አላቸው። ወንድሞቹም ተባሉ።
(ዮሐ. ፯፥፭)
ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው።

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ። ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሣኤ ተመለከቱ። እጆቹን፣ እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ።

ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓት፣ ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው ጌታ ሊቀ ጵጵስናን ሹሟቸው ዐረገ።

ለአሥር ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው። በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን ብርሃናውያን ሆኑ። ሰባ አንድ ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ ሦስት ሺህ ነፍሳትን ማረኩ።
(ሐዋ. ፪፥፵፩)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እስራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል። ከዚህ በኋላ ግን እንደ ትውፊቱ ዓለምን በእጣ ለአሥራ ሁለት ተካፈሏት።

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው። እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ።

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ፣ ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ። በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ። በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ። ለምጻሞችን አነጹ፤ እውራንን አበሩ። አንካሶችን አረቱ። ጐባጦችን አቀኑ፤ ሙታንንም አስነሱ። እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ።

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ። ቆዳቸው ተገፈፈ፤ በምጣድ ተጠበሱ። ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ። ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ። ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን። "አባቶቻችን፣ መምህሮቻችን፣ ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን።

ቅዱስ ማትያስ ስም አጠራሩ ይክበርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰቦቼ ብሎ ከመረጣቸው መቶ ሃያ ቅዱሳን አንዱ፣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን እግር ቁጭ ብሎ የተማረ፣ በይሁዳ ፈንታ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ይቆጠር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ የመረጠው ሐዋርያ ነው።

ቅዱሱ ሐዋርያ በዕጣ በደረሰው ሃገረ ስብከቱና በሌሎቹም ዓለማት ለወንጌል አገልግሎት ብዙ ደክሟል። በተለይ የሰውን ሥጋ ወደሚበሉ ሰዎች ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው ዓይኖቹን አውጥተው ከብዙ ስቃይ ጋር ለሠላሳ ቀናት ሣር አብልተውታል።

እርሱ ግን በትእግስትና በፈጣሪው ኃይል ድንቅ ተአምር አድርጐ አሳምኖ አጥምቋቸዋል። ከብዙ ተጋድሎና ቅድስና በኋላም በዚህች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።

አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ቸርነቱን ያብዛልን። በምልጃቸው ከክፉ ጠብቆ ከበረከታቸው ይክፈለን።

መጋቢት ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)
፪.ቅዱስ አርያኖስ ሰማዕት (በዘመነ ሰማዕታት ብዙ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረና ጌታ በንስሐ የጠራው)
፫.ቅዱስ ዮልዮስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፫.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፬.አቡነ ኪሮስ
፭.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን

".....እንዲህም ብለው ጸለዩ። 'አቤቱ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥከውን አንዱን ግለጥ?' .....ዕጣ አጣጣሉአቸው ዕጣውም በማትያስ ላይ ወጣ። ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋርም ተቆጠረ።"
(ሐዋ ፩፥፳፬-፳፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

መጋቢት ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ተአማኒ (ዘቆረንቶስ)
፪.ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሰማዕት (አማሌቃውያን የገደሉት)
፫.አባ ዘሩፋኤል ጻድቅ
፬.አባ እንጦንስ ገዳማዊ
፭.አባ አርከሌድስ ገዳማዊ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"እውነት እላችኋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል። በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። ደግሞ እላችኋለሁ።..... ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።"
(ማቴ ፲፰፥፲፰-፳)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 በዓለ ጽንሰት <3

ይህች ቀን ለቤተ ክርስቲያን በእጅጉ ልዩ ናት። በዓመቱ ከሚከበሩ በዓላትም አንደኛውን ሥፍራ ትይዛለች።

በዚህች ዕለት አምላካችን እግዚአብሔር
፩.ሰማይና ምድርን ፈጠረ።
(ዘፍ. ፩፥፩)
፪.በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት በድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ (ተጸነሰ)። በዓሉም "በዓለ ትስብእት" ይባላል። "አምላክ ሰው፣ ሰው አምላክ የሆነበት" ማለት ነው።
(ሉቃ. ፩፥፳፮)
፫.የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ።
(ማቴ. ፳፰፥፩ ፣ ማር. ፲፮፥፩ ፣ ሉቃ. ፳፬፥፩ ፣ ዮሐ. ፳፥፩)
፬.ጌታችን ዳግመኛ ለፍርድ በዚህች ቀን ይመጣል።
(ማቴ. ፳፬፥፩)

በእነዚህ ታላላቅና ድርብርብ በዓላት ምክንያት ቀኑ "ርዕሰ በዓላት" (የበዓላት ራስ)፣ "በኩረ በዓላት" እየተባለም ይጠራል።

ቸሩ እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ፣ ከጽንሰቱ፣ ልደቱና ትንሣኤው በረከትን ይክፈለን። በጌትነቱም ሲመጣ በርኅራኄው ያስበን።

ዳግመኛ በዚህች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እልዋሪቆን ገብቷል። ይህች ሃገር የምድራችን መጨረሻ ናት። ከዚያ በኋላ ሰውና ሃገር የለም። እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን የሰበከ ሐዋርያ የለም።

ከቅዱሱ ሐዋርያ ትጋት፣ ቅናት፣ መንፈሳዊነትና ንጽሕና አምላካችን ይክፈለን።

መጋቢት ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ጥንተ ዕለተ ፍጥረት (ዓለም የተፈጠረችበት)
፪.በዓለ ትስብእት (የጌታችን ጽንሰቱ)
፫.ጥንተ በዓለ ትንሣኤ
፬.ዳግም ምጽዐት
፭.ቅድስት ማርያም መግደላዊት
፮.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
፯.ቅዱሳት አንስት (ትንሣኤውን የሰበኩ)
፰.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (ጽንሰታ)
፱.አብርሃ ወአጽብሐ (ጽንሰታቸው)
፲.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ (ጽንሰቱ)
፲፩.ቅዱስ ላሊበላ (ጽንሰቱ)
፲፪.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (ጽንሰታቸው)

ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪.ቅድስት አርሴማ ድንግል
፫.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፭.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)

"እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል። ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል። የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን አሜን።
ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ ይላል።"
(ራእይ ፩፥፯-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"የእሾህ አክሊል ደፍቶ የሞትን ሥልጣን ፍርድ አጠፋ። በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሳለ ከዙፋኑ አልተለየም፤ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አልተለየም። በምድር አይሁድ እንደ በደለኛ ሲዘብቱበት፤ መላእክት በሰማይ የከበረ ጌትነቱን ይናገሩ ነበር።"
(ቅዱስ ኤራቅሊስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የስቅለት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ <3

ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት።
ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አስረው ሲደበድቡት አድረዋል።
ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት።
ምራቃቸውን ተፉበት፤ ዘበቱበት።
ራሱንም በዘንግ መቱት።
እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ።

በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት። በሠለስት (ሦስት ሰዓት ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ገረፉት።
ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። ስድስት ሰዓት ላይ በረዣዥም ብረቶች አምስት ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት። ሰባት ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ።

ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ ሰባት ቃላትን ተናገረ። ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በባሕርይ ሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ።
በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ። አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት።
በዚያች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ። ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ልቅሶን አለቀሰ። ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ።
(ማቴ. ፳፯፥፩ ፣ ማር. ፲፭፥፩ ፣ ሉቃ. ፳፫፥፩ ፣ ዮሐ. ፲፱፥፩)

ለእኛ ለኀጥአን ፍጡሮቹ ሲል ይህንን ሁሉ መከራ የታገሰ አምላክ ስለ አሥራ ሦስቱ ኅማማቱ፣ አምስቱ ቅንዋቱ፣ ስለ ቅዱስ መስቀሉ፣ ስለ ድንግል እናቱ ለቅሶና ስለ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ ብሎ ይማረን።

ከቅዱሳኑ በዚህች ዕለት ከሰማንያ ዓመታት በላይ በገዳም የኖረ የገዳማውያን ሞገሳቸው የመነኮሳትም ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ዐርፏል።

ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) 'ጽድቅ እንደ መቃርስ' የተባለለት፣ የመነኮሳት ሁሉ አለቃ፣ ከሰማንያ ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ፣ በግብጽ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ፣ ከሃምሳ ሺህ በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው።

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብጽ ወደ እስያ በርሃ ከጓደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል። በዚያ ለሁለት ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በኋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሣቸው አጥምቀዋል።

በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ አዕላፍ መላእክትን በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን፣ ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን፣ ማርቆስን፣ ጴጥሮስን፣ ጳውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል። በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።

ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከሁለት ዓመታት ስደትና መከራ በኋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልአኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብጽ መልሷቸዋል። በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከሃምሳ ሺህ በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል።

ስለ ታላቁ ቅዱስ መቃርዮስ ቅድስና ለመጻፍ መነሳት በረከቱ ብዙ ነው። ግን 'ዓባይን በጭልፋ' እንዲሉ አበው ከብዛቱ የተነሳ የሚዘለቅ አይሆንም።

ቅዱስ መቃርስ ከዘመናት በላይ በቆየበት የበርሃ ሕይወቱ፦
፩.አባ ብሶይ፣ አባ ባይሞይ፣ አባ ሳሙኤል፣ አባ በብኑዳን ጨምሮ እርሱን የመሰሉ (ያከሉ) ቅዱሳንን ወልዷል።
፪.ለሕይወታችን መንገድ የሚሆኑንን ብዙ ቃላትን ተናግሯል።
፫.ከገዳማት እየወጣ በብዙ ቦታዎች ቅዱስ ወንጌልን ሰብኳል።
፬.አጋንንትን ድል ከመንሳት አልፎ እንደ ባሪያ ገዝቷቸዋል።
፭.ለዓይንና ጀሮ ድንቅ የሆኑ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል።

በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶችም ቤተ ክርስቲያን "ርዕሰ መነኮሳት (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)" ስትል ትጠራዋለች። በዘጠና ሰባት ዓመቱ መጋቢት ፳፯ ቀን ሲያርፍ መላእክት ብቻ ሳይሆን አጋንንትም ስለ ድል አድራጊነቱ ዘምረውለታል።

ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በኋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ። ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ ይባላሉ።) የኖሩባት ቦታ ናት። የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው።

በምድረ ግብጽ በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር። መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር አንድም ለበረከት (በረከትን ሲሹ) አደረጉት።

ወደ ሳስዊርም ወስደው ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት። በዚያም ለመቶ ስልሳ ዓመታት ተቀመጠ። በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ። በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ። በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት።

በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ። አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት በነበረበት ዘመን ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ።

ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና። ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላችኋለን።" ብለው ሰይፍ፣ ዱላ፣ ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው።

መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ። መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራእይ ተቆጣው። በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ።

ሕዝቡም በዝማሬና በማኅሌት ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው። ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ። ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል።

አምላከ ቅዱሳን የታላቁ ቅዱስ መቃርስን ትሕትናውን፣ ትእግስቱንና ቅንነቱን ያድለን። በበረከቱም ይባርከን።

ዳግመኛ በዚህ ቀን ንግሥናን ከሊቅነት ጽድቅን ከሰማዕትነት ጋር የደረበው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዴዎስ አንገቱን ተከልሏል። ቅዱስ ገላውዴዎስ የጻድቁ ዐፄ ልብነ ድንግል ልጅ ነው።

መድኃኔ ዓለም ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዘመነ ሐጋይ (በጋ) የመጨረሻ ዕለትና ለሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን ሥነ ፍጥረት የፈጠረ ለሰው ልጆች ጥቅም ነው። ጌታ አዝማናትን፣ ወሮችን፣ ሳምንታትን፣ ቀኖችንና ሰዓታትን ፈጥሮ ወስኖ ሰጥቶናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት እንደ መሆኗ ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ይፈፀማል።

በራሷ የዘመን ቀመር ስሌት መሠረትም አንድ ዓመት በአራት ወቅቶች ይከፈላል። አባታችን ሊቁ ቅዱስ ያሬድም እነዚህን ወቅቶች መሠረት አድርጎ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል።

እነዚህ አዝማናት (ወቅቶች)፦
፩.ዘመነ ክረምት (ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭)
፪.ዘመነ መፀው (ከመስከረም ፳፮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭)
፫.ዘመነ ሐጋይ (ከታኅሣሥ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፭)
፬.ዘመነ ፀደይ (ከመጋቢት ፳፮ እስከ ሰኔ ፳፭) መሆናቸው ይታወቃል።

ዘመነ ሐጋይ (በጋን) የባረከ አምላክ ዘመነ ፀደይ (መከርን) እንዲባርክልን የንስሐ ጊዜም እንዲያደርግልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን።

<3 ቅዱስ አንሲፎሮስ <3

በዚህች ዕለት ጌታችንን በሃገረ ናይን የተከተለ ከዋለበት ውሎ ካደረበት ያደረ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ ዐርፏል።

ዳግመኛ በዚህች ዕለት አይሁድ ለመጨረሻ ጊዜ ጌታችንን ሊገድሉት ተስማሙ። ይሁዳም በሠላሳ ብር ይሸጠው ዘንድ ከአይሁድ ጋር ተዋዋለ።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን ጋር ይሁን።

መጋቢት ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አንሲፎሮስ ሐዋርያ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፮.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

"ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን። እርሱም..... ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።"
(ዕብ ፩፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ተአምር ሠሪው ሰማዕት ሆይ! ትግልህ ሕይወት ሥነ ተጋድሎህም መድኃኒት ይሆነኝ ዘንድ ፈጽሜ እማልድሃለሁ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ በዓለ ሆሣዕና በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጥንተ በዓለ ሆሣዕና <3

"ጥንተ በዓል" ማለት በዓሉ ተአምሩ (የማዳን ሥራው) የተፈፀመበት የመጀመሪያው ቀን ማለት ነው። በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሆሣዕና ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያሉ ዐበይት በዓላትን ሁለት ጊዜ ታከብራለች።
፩ኛው. "ጥንተ በዓል" ሲሆን
፪ኛው. ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሰኛል።
መሠረቱ የቅዱሳን ሐዋርያት ቀኖናና የአባታችን የድሜጥሮስ መንፈሳዊ ቀመር ነው።

ስለሆነም ዓለም ከተፈጠረ በአምስት ሺህ አምስት መቶ ሠላሳ አራት ዓመት ልክ በዛሬዋ ቀን (መጋቢት ፳፪) ስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና በአህያዋና በውርንጫዋ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም (ቤተ መቅደስ) ገብቷል።

ታላቅ የምስጋና መስዋዕትም ከመላእክት፣ ከሐዋርያት፣ ከሕፃናት፣ ከአረጋውያን፣ ከፀሐይ፣ ከጨረቃ፣ ከከዋክብት፣ ከቢታንያ ድንጋዮች..... በአጠቃላይ ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ቀርቦለታል። ጌትነቱንም በገሃድ ገልጧል።

ከበዓሉ በረከት ይክፈለን። እኛንም ለጣዕመ ምስጋናው የተዘጋጀን ያድርገን።

<3 ቅዱስ ቄርሎስ መንፈሳዊ <3

የቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ጳጳስ የነበረ ንጽሕናው የተመሠከረለት አባት ሲሆን በ፫፻፹፩ ዓ.ም በቁስጥንጥንያ ከተሠበሠቡ መቶ ሃምሳ ቅዱሳን ሊቃውንት አንዱ ነው። ብዙ ድርሳናትንም ጽፏል።

መጋቢት ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ንጹሐን አርድእትና ቅዱሳት አንስት (የጌታችን መቶ ሃያ ቤተሰቦች)
፪.ቅዱስ ቄርሎስ መንፈሳዊ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፬.አባ እንጦንዮስ (አበ መነኮሳት)
፭.አባ ጳውሊ የዋህ

"አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ። አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ። እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው። ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።"
(ዘካ ፱፥፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት ላስነሳበት ደግ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሐዋርያ ቅዱስ አልዓዛር <3

ከቀናት በፊት ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ አልዓዛር ዐረፈ ብለን ነበር። ለስም አጠራሩ ስግደት፣ ክብር፣ ጌትነት ይድረሰውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛር ባረፈ በአራተኛው ቀን ወደ ቢታንያ ደረሰ።

ማርታ ቀድማ ወጥታ ከእንባ ጋር ተቀበለችው።
"አዳም ወዴት ነህ?" ያለ (ዘፍ. ፫፥፲) የአዳም ፈጣሪ "አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት?" አለ። ቸርነቱ፣ ባሕርዩ ያራራዋልና ማርያም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አብሮ አለቀሰ።

ከዚያም በባሕርይ ሥልጣኑ "አልዓዛር! አልዓዛር!" ብሎ አልዓዛርን አስነሳው። ይህች ተአምርም በአይሁድ ዘንድ ግርምት ሆነች። ለጌታም የሞት ምክንያት አደረጓት። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ እንዲህ ታስተምራለች።
(ዮሐ. ፲፩፥፩ - ፍጻሜው)

ቅዱስ አልዓዛር ጌታችን ካስነሳው በኋላ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ (ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ነውና።) ለአርባ ዓመታት ወንጌልን አስተምሮ በ፸፬ ዓ.ም አካባቢ ቆጵሮስ ውስጥ ዐርፏል።

የጌታችን ቸርነቱ የአልዓዛር በረከቱ ይድረሰን።

መጋቢት ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አልዓዛር ጻድቅ ሐዋርያ (የጌታ ወዳጅ)
፪.ቅድስትና ብጽዕት ሰማዕት አስጠራጦኒቃ (ከታላላቅ ሰማዕታት አንዷ)
፫.ቅዱሳን ሰማዕታት (የቅድስት አስጠራጦኒቃ ማኅበር)
፬.እናታችን ቅድስት ጽጌ ሥላሴ (ኢትዮጵያዊት)
፭.ቅዱስ አስቃራን ሰማዕት
፮.አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፫.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፬.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፭.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፮.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

"ጌታ ኢየሱስም 'ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?' አላት።..... ይህንም ብሎ በታላቅ ድምጽ 'አልዓዛር ሆይ ወደ ውጭ ና።' ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ። ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ጌታ ኢየሱስም 'ፍቱትና ይሂድ ተውት።' አላቸው።"
(ዮሐ ፲፩፥፵-፵፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ኤስድሮስ <3

ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው። ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል። ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው።

ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል። የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው።
"አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም። ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት።" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው።

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ!

በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ። ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም።

እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ። የሚረግሟችሁን መርቁ። ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ።" ብሎናልና።
(ማቴ. ፭፥፵፬)
ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል።

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል። የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና።

ቤተ ክርስቲያናችን ኢትዮጵያዊውን የጐንደር ዘመን ሊቅ ጨምሮ በዚህ ስም የምትዘክራቸው አያሌ ቅዱሳንና ሊቃውንት አሏት።

ዛሬ የምናከብረው ሰማዕቱ ቅዱስ ኤስድሮስ በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ቅዱስ ፃና የሚባል ደግ ጓደኛ የነበረው ሁለቱንም እናቶቻቸው እንደሚገባ ያሳደጓቸው የሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ነበሩ።

በወጣትነት ዘመናቸው በድንግልና ቅዱስ ፃና የሠራዊት አለቃ ቅዱስ ኤስድሮስ ደግሞ የልብስ ዝግጅት ባለሙያ ነበሩ። ከሚያገኙት ገቢ ለዕለት ጉርስ ብቻ እያስቀሩ ለነዳያን ይመጸውቱ ነበር።
በመከራ ዘመን (ዘመነ-ሰማዕታት) ቅዱሳኑ ያላቸውን ሁሉ ለነዳያን አካፍለው በክርስቶስ ስም መሞትን መርጠዋል።

በዚህች ቀንም አስቀድሞ ቅዱስ ኤስድሮስ አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀዳጅቷል።

ፈጣሪ ከሰማዕቱ ክብር ያድለን።

መጋቢት ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
፫.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

"የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ። ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ .....አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።
ሰባኪው "ከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው።" ይላል።"
(መክ ፲፪፥፩-፱)

"ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ። ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ። ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።"
(፩ጴጥ ፬፥፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት <3

አባ ሚካኤል በትውልዳቸው ግብጻዊ ሲሆኑ ገና በሕፃንነታቸው ገዳማዊ ሕይወትን መርጠው ለዓመታት በተጋድሎ ገዳመ አስቄጥስ ውስጥ ኑረዋል። በዘመኑ ግብጽ ሊቀ ጳጳሷ ዐርፎባት ነበርና በሱባዔ እያሉ "አባ ሚካኤልን ሹሙት።" የሚል ቃል ከሰማይ ሰምተው "እንሹምህ" አሉት። "እንቢ" ቢላቸው ግድ ብለው አስረው ሹመውታል።

አባ ሚካኤል በመንበረ ማርቆስ ላይ እረኝነት (ጵጵስና) ተሹሞ ጭንቅ ጭንቅ መከራዎችን ተቀብሏል። በወቅቱ የነበረው የግብጽ ከሊፋ (አባቶቻችን ክፉ ሰው ማለት ነው ይላሉ።) አባ ሚካኤልን አሥሮ በሕዝቡ ፊት ይደበድባቸው ነበር።

ከመከራው ብዛት የተነሳ በርካቶቹ ተገደሉ፤ ከሃያ ሺህ በላይ ምዕመናን ሃይማኖታቸውን ካዱ።
ይህንን የሰሙት የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ በመንፈሳዊ ቅንዐት መቶ ሺህ ፈረሰኛ፣ መቶ ሺህ በበቅሎ፣ መቶ ሺህ ሠራዊት በግመል ጭነው ወደ ግብጽ ወርደው ከሊፋውን አስጨንቀው የግብጽን ክርስቲያኖች ከመከራ ታድገዋል።

አባ ሚካኤልም ከእሥር ከተፈቱ በኋላ የካዱ ምዕመናንን ለመመለስ ብዙ ደክመዋል፤ ተሳክቶላቸውማል። ጻድቁ ሊቀ ጳጳሳት ከዓመታት ተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፈዋል።

ፈጣሪ ከበረከታቸው አይንሳን።

መጋቢት ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
፬.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፯.አባ ዳንኤል ጻድቅ

"በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሠር አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።
.....የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።"
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ <3

ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ብዙ መከራን በማሳለፉና የጌታችንን ጐን በመዳሰሱ ይታወቃል።

ቅዱስ ቶማስ እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት በእስራኤል ተወልዶ በዚያውም በሥርዓተ ኦሪት አድጐ ገና በወጣትነቱ የሰዱቃውያንን ማኅበር ተቀላቅሏል። ሰዱቃውያን ሰው ከሞተ በኋላ አይነሳም (አልቦ ትንሣኤ) የሚሉ ናቸው። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተማር ሲጀምር ግን ቅዱስ ቶማስ ከነበረበት ማኅበር ወጥቶ ጌታችንን ተከተለ። ጌታችንም ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ይሆን ዘንድ ሾመው። የቀደመ ስሙ "ዲዲሞስ" ሲሆን ጌታችን "ቶማስ" ብሎታል።

ቅዱስ ቶማስ ጌታ አልዓዛርን ለማስነሳት በሔደ ጊዜ ሌሎች ሐዋርያት ጌታን "አይሁድ ይገድሉሃል ቅር።" ሲሉት እርሱ ግን "እንሒድና አብረን እንሙት።" ሲል ፍቅሩን አሳይቷል።
(ዮሐ. ፲፩፥፲፮)

ጌታችን ትንሣኤውን ለደቀ መዛሙርቱ በገለጠ ጊዜ ያልነበረው ቶማስ ካላየሁ አላምንም አለ። ምክንያቱም፦
፩.ለጌታችን ከነበረው ፍቅር የተነሳ እውነት አልመስልህ ቢለው፣
፪.አንድም ሌሎቹ ሐዋርያት "ትንሣኤውን አየን።" እያሉ ሲያስተምሩ እኔ ግን "ሰማሁ" ብየ ማስተማሬ ነው ብሎ በማሰቡ ነበር።

ለጊዜው ጌታ ተገልጾ ቢገስጸው "እግዚእየ ወአምላኪየ (ጌታዬና አምላኬ)" ብሎ ፍጹም ሃይማኖቱን ገልጿል። ለፍጻሜው ግን የጌታችንን ጎን (መለኮትን) ይዳስስ ዘንድ ባለቤቱ እንዳደለው ያጠይቃል። መለኮትን የዳሰሰች ይህች ቅድስት እጁ ዛሬም ድረስ ሕያው ናት። በሕንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም በክብር ተቀምጣለች።

ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ሐገረ ስብከት ሲከፋፈሉ ለቅዱስ ቶማስ ሕንድና በዙሪያዋ ያሉ ሃገራት ደረሱት። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ዘርዝረን የማንጨርሰውን ተጋድሎ የፈጸመው። ቅዱሱ በነበረው ፍጹም ትጋት አባቶቻችን "ዘአሠርገዋ ለብሔረ ሕንደኬ (ሕንድን በወንጌል ያስጌጣት)" ሲሉ ያከብሩታል።

ቅዱስ ቶማስ ንጉሥ ሉክዮስንና የሃገሩን ሕዝብ ለማሳመን በችንካር መሬት ላይ ወጥረው ቆዳውን ገፈውታል። ቆዳውንም እንደ ገና ሰፍተው አሸዋ ሞልተው አሸክመውታል። በየመንገዱ የተገፈፈ ገላውን ጨው ቢቀቡት በጎች መጥተው ግጠው በልተውታል። በዚህ ምክንያት፦
"ኩሉ የአኪ እንዘ የአኪ ዘመኑ
አባግዒሁ ለቶማስ እስመ አራዊተ ኮኑ።" ብለዋል ሊቃውንቱ።

በኋላ ግን ከፎቅ ወድቃ የሞተችውን የንጉሡን ሚስት በተገፈፈ ቆዳው በማዳኑ ሁሉም አምነው ተጠምቀዋል።

ቅዱሱ ሐዋርያ ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አንዳንዴ በፈሊጥ ሌላ ጊዜም በመከራ ለወንጌልና ለቤተ ክርስቲያን ተጋድሏል። ያለ ማቋረጥም ከሕንድ እስከ ሃገራችን ኢትዮጵያ ድረስ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ወንጌልን ሰብኳል።

በመጨረሻም በ፸፪ ዓ.ም በሰማዕትነት ዐርፏል። መቃብሩና ቅድስት እጁ ዛሬ ድረስ ሕንድ ውስጥ አሉ። ከኘሮቴስታንቶች በቀር መላው ዓለም ያከብረዋል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአገልጋዩ ቅዱስ ቶማስ ጸጋ በረከት ይክፈለን።

መጋቢት ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ (ጋኔን ያደረባት ሴትን ፈውሶ አሕዛብን ያሳመነበት)
፪.ቅዱስ አባ ባጥል ትሩፈ ምግባር (ባንድ ወቅት ከእስክንድርያ ዝሙትን ለማጥፋት የተጋደሉ ጻድቅና አረጋዊ አባት)
፫.ቅዱስ ሲኖዳ (ሺኖዳ) ሰማዕት
፬.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

"ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ። በመካከላቸውም ቆሞ 'ሰላም ለእናንተ ይሁን።' አላቸው። ከዚያም በኋላ ቶማስን 'ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ። እጅህንም አምጣና በጐኔ አግባው። ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን።' አለው። ቶማስም 'ጌታዬ አምላኬም' ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም 'ስላየኸኝ አምነሃል። ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው።' አለው።"
(ዮሐ ፳፥፳፮-፳፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ድሜጥሮስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ድሜጥሮስ ድንግል <3

ቅዱስ ድሜጥሮስ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተወለደ በመንፈሳዊ ለዛ ከአጐቱ ደማስቆስ ጋር ያደገ የዘመኑ ደግ ሰው ነበር። በዘመኑ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ያለቁበት በመሆኑ ቤተሰቦቹ የአጎቱን ልጅ ልዕልተ ወይንን እንዲያገባ ግድ አሉት።

ቅዱስ ድሜጥሮስ የእነርሱን ፈቃድ ለመፈፀም ጋብቻውን በተክሊል ፈፀመ። የፈጣሪውን ፈቃድ ለመፈፀም ደግሞ ከቅድስት እናታችን ልዕልተ ወይን ጋር ተስማምተው ለአርባ ስምንት ዓመታት በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ አንድ ምንጣፍና ልብስ እየተጋሩ በድንግልና ኑረዋል።

ቅዱስ ሚካኤልም ስለ ክብራቸው ከመካከላቸው ሆኖ ቀኝ ክንፉን ለእርሱ ግራ ክንፉን ለእርሷ ያለብሳቸው ነበር። ከአርባ ስምንት ዓመታት በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ የግብጽ አሥራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሹሞ ምሥጢር በዝቶለት ባሕረ ሐሳብን ጽፎ ሠርቷል።

ሰይጣን በሰዎች አድሮ ቅዱሱን ሚስት አለው በሚል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከት በመፈጠሩ ቅዱስ ድሜጥሮስ በመልአኩ ትእዛዝ ሕዝቡን ሰብስቦ እሳት አስነድዶ ከቅድስት ልዕልተ ወይን ጋር እሳቱ ውስጥ ገብተው ለረዥም ሰዓት ጸልየዋል።

ሕዝቡም ይህን ተአምር አይተው የቅዱሳኑን ንጽሕና ተረድተው "ማረን" ብለው በፍቅር የተለያዩት በዚህች ዕለት ነው።

ቅዱስ ድሜጥሮስና እናታችን ልዕልተ ወይን ተረፈ ዘመናቸውን በቅድስና አሳልፈዋል። በተለይ ሊቀ ጳጳሳቱ ድሜጥሮስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል። እነ አርጌንስ (Origen)ና ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ (Clement of Alexandria) የመሰሉ መናፍቃንንም አውግዟል።

ከጣዕመ ስብከቱም የተነሳ አርጅቶ እንኳ ምዕመናን እየተሰበሰቡ ይማሩ ነበር። በአልጋ ተሸክመውም ይባርካቸው ነበር። ቅዱሱ በመቶ ሰባት ዓመቱ ያረፈው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነው።

አምላከ ድሜጥሮስ ንጽሕናውን ያሳድርብን። ጸጋ በረከቱን ደግሞ ያትረፍርፍልን።

መጋቢት ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት (ደንግልናው የተገለጠበት)
፪.ቅድስት ልዕልተ ወይን
፫.ቅዱስ መላዚ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት (ጠንቋዩን በለዓምን የገሰጸበትና አህያዋን እንድትናገር ያደረገበት)
፪.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፭.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፮.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

"ሥጋዊ ፈቃዳቸውን የሚሠሩ ሁሉ እነርሱ በላይኛው ዓለም የሞቱ ናቸው። ግን በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ድል ከነሳችሁት ለዘላለም በሕይወት ትኖራላችሁ። የእግዚአብሔር መንፈስ የሚወደውን ሥራ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።"
(ሮሜ ፰፥፲፫-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

“ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ፅፀ መድኃኒት ኃይልነ ወጸወንነ”

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ኩትን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሐዋርያው ቅዱስ ኩትን <3

ቅዱስ ኩትን በዘመነ ሐዋርያት የነበረ፣ ከአሕዛብ ወደ ክርስትና በቅዱስ ጳውሎስ አማካኝነት የተመለሰ፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት እግር ሥር ቁጭ ብሎ ይማር ዘንድ የታደለ፣ በፍፁም ድንግልናው የተመሰገነ ሐዋርያዊ አባት ነው።

ይህ ቅዱስ ሚስት ነበረችው። ግን በትዳር ውስጥ ሆኖ ድንግልናን መጠበቅ እንደሚቻል ያሳየ የሐዲስ ኪዳን ሰው ነው። ቅዱስ ኩትን በንጽሕናው፣ በአገልግሎቱና በጣዕመ ስብከቱ በሐዋርያትና ምዕመናንም ተወዳጅ ነበር። ለብዙ ዘመናት በወንጌል አገልግሎት ኑሮ በዚህች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።

ፈጣሪ ከበረከቱ ያድለን።

መጋቢት ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኩትን ሐዋርያ
፪.ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት
፬.ሁለት ሺህ ሰማዕታት (የአባ ኖብ ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
፫.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
፬.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
፮.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

".....ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር የወደደውን ያድርግ። ቢያገባም ኃጢአት የለበትም። ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም። የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል። ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና መልካም አደረገ። እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ። ያላገባም የተሻለ አደረገ።"
(፩ቆሮ ፯፥፴፮-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ቀዳማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ እና ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጻድቁ ንጉሥ ቴዎድሮስ <3

በሃገራችን ታሪክ በጣም ተወዳጅ ከነበሩ ነገሥታት ጻድቁ ቴዎድሮስ ቅድሚያውን ይወስዳል። በርግጥ በርካቶቻችን የምናውቀው ስለ ሃገሩ ፍቅር ራሱን የሰዋውን ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን (፲፰፻፵፭ - ፲፰፻፷) ነው። በበጎ ሥራውና በቅድስና ሕይወቱ የተመሠከረለት ግን ዛሬ የምናስበው ቀዳማዊው ነው።

ቀዳማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የደጉ ዐፄ ዳዊት (ግማደ መስቀሉን ያመጡት)ና የተባረከችው ሚስታቸው ጽዮን ሞገሳ ልጅና የጻድቁ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ታላቅ ወንድም ነው። በኢትዮጵያ ለሦስት ዓመታት (ከ፲፫፻፺፮ - ፲፫፻፺፱) ብቻ ነግሦ እያለ እንደ ንጉሥ ሳይሆን፦
ከጠዋት እስከ ማታ ድሃ እንዳይበደል ፍርድ እንዳይጓደል ይታትር የነበር፣
ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር፣
ወገቡን ታጥቆ ነዳያንን የሚያበላ፣
ለአብያተ ክርስቲያናትም የሚጨነቅ ደግ ሰው ነበር።
ስለዚህም በሕዝቡ እጅግ ተወዳጅ ነበር። በነገሠ በሦስት ዓመቱ ዐርፎ በዝማሬና በለቅሶ ሥጋውን ተሸክመው ሲሔዱ ወንዝ ተከፍሎላቸዋል። ከመቃብሩም ላይ ጠበል ፈልቋል።

<3 ቅዱስ ቴዎዶጦስ <3

በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ጊዜው ለክርስቲያኖች ሁሉ ፍጹም የመከራ ከመሆኑ የተነሳ "ዘመነ ሰማዕታት" ሲባል በወቅቱ ከአርባ ሰባት ሚሊየን በላይ ክርስቲያኖች ተጨፍጭፈዋል።

የዘመኑ ክርስቲያኖች ለመሞት የሚያደርጉትን እሽቅድምድም እያዩ አሕዛብ "ወፈፌዎች" እያሉ ይጠሯቸው ነበር። (ዓለም እንዲህ ናትና!) እብዶቹ ጤነኞችን "እብድ" ማለታቸውኮ ዛሬም አለ። (ለነገሩ "ግደልና ጽደቅ" ከሚል መመሪያ በላይ ጤና ማጣት አይኖርም።)

ታዲያ በወቅቱ አንድ ቴዎዶጦስ የሚሉት ወጣት በምድረ ግብጽ ይኖር ነበር። ወጣቱ እጅግ ብርቱ ክርስቲያን ነበርና እንደ ዘመኑ ልማድ ተከሶ በነፍሰ ገዳዮች ፊት ቀረበ። ክሱ አንድ ብቻ ነው። "ክርስቶስን አምልከሃል።" የሚል።

ከሥጋ ሞት ለማምለጥ ደግሞ መንገዱ ያው አንድ ብቻ ነው። ፈጣሪውን ክርስቶስን ክዶ ለአሕዛብ አማልክት (አጋንንት) መገዛት። ቅዱስ ቴዎዶጦስ በገዳዮቹ ፊት ቆሞ ተናገረ። "እኔ ክርስቲያን፣ ክርስቶሳዊ፣ የክርስቶስ ነኝ። ምንም ብታደርጉኝ ከክርስቶስ ፍቅር ልትለዩኝ አትችሉም።"አላቸው።
(ሮሜ. ፰፥፴፭)

እነሱ ግን ነገሩ እውነት አልመሰላቸውምና ሊያሰቃዩት ጀመሩ።
ገረፉት፣
አቃጠሉት፣
ደበደቡት፣
ሌላም ሌላም ማሰቃያዎችን በእርሱ ላይ ተጠቀሙ። የሚገርመው ግን እርሱ ሁሉን ሲታገሥ ገዳዮቹ ግን ደከሙ።

በመጨረሻም ወደ ገዢው ዘንድ አቅርበው "ብዙ አሰቃይተነዋል፤ ግን ሊሳካልን አልቻለም።" በሚል ሰይፍ (ሞት) ተፈረደበት። በአደባባይ ሊሰይፉት ሲወስዱት ግን ትንሽ አዘኑለት መሰል ጨርቅ አምጥተው "ፊትህን ሸፍን።" አሉት። (ያኔ ትንሽም ቢሆን ሰብአዊነት ሳይኖር አይቀርም።)

ቅዱስ ቴዎዶጦስ ግን ገዳዮቹን በመገረም እየተመለከታቸው ተናገረ "እኛ ክርስቲያኖች ሞትን አንፈራም። ሞት ለእኛ ወደ ክርስቶስ መሸገጋገሪያ ድልድያችን ነውና የምንፈራው ሳይሆን የምንናፍቀው ነው።" "ኢትፍርሕዎሙ (አትፍሯቸው)።"
(ማቴ. ፲፥፳፰)

ይህን ብሎ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ጌታውን አመሰገነ። ፊቱ ላይ ደስታ እየተነበበ ጨካኞቹ አንገቱን ሰየፉት። በብርሃን አክሊልም ቅዱሳን መላእክት ከለሉት።

መሠረታዊው ነገር ቅዱስ ቴዎዶጦስ ለምን አልፈራም? ነው።
አጭር መልስ ካስፈለገን ቅዱሱ ያልፈራው ከልቡ ክርስቶሳዊ በመሆኑ ነው። ትኩረት እንድንሰጠው የሚያስፈልገው ግን የሰማዕታት ምሥጢራቸው፦
፩.በጽኑ የክርስትና መሠረት ላይ መመሥረታቸው፣
፪.ዕለት ዕለት የክርስቶስን ፍቅር መለማመዳቸው፣
፫.ከወሬ (ንግግር) ይልቅ ተግባርን መምረጣቸው፣
፬.በንስሐ ሕይወት መመላለሳቸው፣
፭.ሥጋ ወደሙን የሕይወታቸው ዋና አካል ማድረጋቸው፣
፮.ከእነርሱ የቀደሙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት ከልብ ማንበባቸው፣
፯.በቃለ እግዚአብሔር መታነጻቸው….. መጠቀስ የሚችሉ መገለጫዎቻቸው ናቸው።

ዛሬ ዓለማችን ከጠበቅነው በላይ ነፍሰ በላነቷ እየጨመረ ነው። ዛሬ የክርስትና ጠላቶች ከጉንዳን በዝተዋል።
የራሳችን ማንነት፣
ክርስትናችን በአፋችን ላይ ብቻ መሆኑ፣
እረኞችና በጐች መለያየታቸው….. ሁሉ እኛ ልናርማቸው የሚገቡ ናቸው።
አሸባሪዎች፣
አሕዛብ፣
የመዝናኛው ዓለም፣
ሰይጣን አምላኪ ዝነኞች (Celebrities)፣
ሚዲያው፣
ማኅበራዊ ድረ ገጾችና መሰል ነገሮች ደግሞ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡና እኛን ውስጥ ለውስጥ በልተው የፈጁን የሰይጣን መሣሪያዎች ናቸው።

ስለዚህም ከዛሬ ጀምረን ባለ መታወክ ክርስትናችንን ከአፋችን ወደ ልባችን፣ ከብዕራችን ወደ አንጀታችን እንድናወርደው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላለች።

ዛሬ ነገሮችን ረስተን ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን ከጀመርን እጅግ አሳፋሪ መሆኑ አይቀርም። በጐውን ጐዳና ተከትለን በሃይማኖትና በፍቅረ ክርስቶስ ከጸናን ግን ማንም ቢመጣም ፈጽሞ አንናወጥም።

ይልቁኑ "አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህም ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።" (መዝ. ፵፮፥፩) እያልን ከቅዱስ ዳዊት ጋር እንዘምራለን።

ለዚህ ደግሞ ደመ ሰማዕታት ይርዳን። በረከታቸው ይድረሰን። የጌታ ፍቅርም አይለየን።

ዘላለም ሥላሴ ደግ መሪና ሰላማዊ ዘመንንም ያድሉን።

መጋቢት ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ጻድቁ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ዐፄ ቴዎድሮስ
፪.ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት
፬.ቅዱስ አብላንዮስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

"ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና። ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል። …..ለሁሉ እንደሚገባው አስረክቡ። ግብር ለሚገባው ግብርን፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ።"
(ሮሜ. ፲፫፥፩-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ቴዎዶስዮስ ተአማኒ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቴዎዶስዮስ <3

በሃገረ ኒቅያ በእመቤታችን እና በአምላክ ልጇ የሚያምኑ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ተሰብስበዋል። ከእነዚህ አንዱ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ እንደሆነ በትውፊት ይታመናል። የጉባዔውስ ነገር እንደምን ነበር ቢሉ፦
የሊብያው ሰው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ስምንት ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ።

ጥሪው የተላለፈው በወርኀ ሚያዝያ ሲሆን በመንገድ ችግር ሁሉም ተጠቃለው ኒቅያ የገቡት መስከረም ፳፩ ቀን ነበር። ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና ምግባራቸው የጸና ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ።

እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው። እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና በመገለጫ እንመልከት:-
፩.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (በዘመነ ሰማዕታት ለሃያ ሁለት ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ፣ እግር፣ ጀሮ፣ ከንፈር፣ ቅንድብ ነው።)
፪.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ (ስለ ቀናች እምነት ለሃምሳ ዓመታት የተጋደለና ለአሥራ አምስት ዓመታት በስደት የኖረ ነው።)
፫.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው።)
፬.ቅዱስ ቴዎዶስዮስ (በምድረ ቆረንቶስ መከራን የተቀበለ አባት ነው።)
፭.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ (በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ፣ ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው።)
፮.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ (ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጓድ ውስጥ ለአሥራ አምስት ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው።)
፯.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ (ከሕፃንነቱ የተቀደሰ፣ በበርሃ የተጋደለ፣ በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው።)
፰.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ፣ ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ፣ በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው።)
፱.ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ (ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው።)
፲.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ (ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው።)

ለአብነት እንዲሆኑን እነዚህን አነሳን እንጂ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱም ሊቃውንት ስለ ቤተ ክርስቲያን ተግተው የተጋደሉ ብዙ ዋጋም የከፈሉ አባቶች ናቸው።

በወቅቱ ታዲያ ቤተ ክርስቲያንን የበጠበጡ ብዙ መናፍቃን ቢኖሩም የአርዮስ ግን ከመጠኑ አለፈ። የእርሱ ኑፋቄ (ፈጣሪያችንን ፍጡር ማለቱ) መነሻው ከእርሱ በፊት ነው። መናፍቃን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ መኖራቸው ግልጽ ነው።

በተለይ ደግሞ ቢጽ ሐሳውያንና ግኖስቲኮች የወለዷቸው እሾሆች አባቶቻችንን እንቅልፍ ነስተው ነበር። የሚገርመኝ በዘመኑ እንደ ነበሩ መናፍቃን ኃይለኝነት የእኞቹ ከዋክብት ሊቃውንት ባይኖሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያሳስብ ነበር።

ግን እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሚገባ ያዘጋጃልና አበው ብርቱ መናፍቃንን በብርቱ መንፈሳዊ ክንድ እያደቀቁ ከጐዳና አስወገዷቸው። የዛሬውን ደካማ ትውልድ ደግሞ የአርዮስ ልጆች ሁለትና ሦስት ጥቅስ ይዘው ሲያደናብሩት ይውላሉ።

ሐረገ መናፍቃን በርጉም ሳምሳጢ ጳውሎስ፣ በመርቅያንና በማኒ ይጀምራል። በእርግጥ አርጌንስ እና የግብጹ ቀሌምንጦስም ተቀላቅለዋቸዋል። ርጉም ሳምሳጢ ድያድርስን በኑፋቄ ወልዶታል። ድያድርስ ሉቅያኖስን ሉቅያኖስ ደግሞ አርዮስን ወልደዋል።

ይህ አርዮስ እጅግ ተንኮለኛ በመሆኑ ልክ እንደ ዘመኑ መሰሎቹ ግጥምና ዜማ እየጻፈ በየመንገዱ እያደለ በየቤቱ እየሰበከ ብዙዎችን በኑፋቄው በከለ። በመጀመሪያ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ (አስተማሪው) መከረው። ባይሰማው ከአንዴም ሁለት ጊዜ አወገዘው።

ቆይቶ ሰነፉ ጳጳስ አኪላስ ቢፈታውም ሊቁ ቅዱስ እለእስክንድሮስ እንደ ገና አወገዘው። እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት!) ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው።

ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ (ኢሳ. ፱፥፮ ፣ መዝ. ፵፮፥፭ ፤ ፸፯፥፷፭ ፣ ዘካ. ፲፬፥፬ ፣ ዮሐ. ፩፥፩ ፤ ፲፥፴ ፣ ራእይ. ፩፥፰ ሮሜ. ፱፥፭) አርዮስና የዛሬ መሰሎቹ አንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል።

በወቅቱም በመወገዙ "ተበደልኩ" ብሎ የጮኸው አርዮስ ከሁለቱ አውሳብዮሶች ባልንጀሮቹ (ዘቂሣርያና ዘኒቆምድያ) ጋር ሆኖ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ። ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውንት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ።

ከሚያዝያ ፳፩ እስከ መስከረም ፳፩ ተጠቃለው ገቡ። በ፫፻፳፭ ዓ.ም (በእኛው በ፫፻፲፰ ዓ.ም) ለአርባ ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ። ሱባኤውን ሲጨርሱም በአራቱ ፓትርያርኮች (እለእስክንድሮስ፣ ሶል ጴጥሮስ፣ ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ) መሪነት በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ።

በጉባኤው ሙሉ ሥልጣን በሰማይ ከፈጣሪ በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት። ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ፣ ሥግው ቃል፣ ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት።
በጉባኤው መጨረሻም፦
፩.አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ።
፪.ጸሎተ ሃይማኖትን "ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።" እስከሚለው ድረስ ተናገሩ።
፫.ፍትሐ ነገሥትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ብለው አዘጋጁ።
፬.ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ።
፭.በስማቸው የሚጠራ አንድ ቅዳሴን ደረሱ።

ይህ ሁሉ ሲሆን መድኃኒታችን ክርስቶስ ሦስት መቶ አሥራ ዘጠነኛ ሆኖና ገሊላዊ ጳጳስን መስሎ ሁሉን አከናውኖላቸዋል። አባቶችም ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል። ለክብረ መንግሥተ ሰማያት በቅተዋል።
እኛም እነሆ "አባቶቻችን፣
መምህሮቻችን፣
መሠረቶቻችን፣
ብርሃኖቻችን፣
ምሰሶዎቻችን" እያልን እናከብራቸዋለን።

ቅዱስ ቴዎዶስዮስ የቆረንቶስ ጳጳስ ሲሆን በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን አሳልፎ ከሰማዕታት ተቆጥሯል። ነገር ግን አልተሰየፈም ነበርና እስከ ጉባኤ ኒቅያ ቆይቶ የጉባኤው ተሳታፊ ሆነ።

ከጉባኤው በኋላ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ወደ ሃገሩ ቆረንቶስ ተመልሶ ሕዝቡን ሲመክር ቆይቶ በዚህች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።

አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን።

Читать полностью…
Subscribe to a channel