gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ብሩታዎስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ብሩታዎስ <3

ሐዋርያው ቅዱስ ብሩታዎስ በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው የውዳሴ ማርያም ደራሲ ነው።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፦
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ ሙቶ ከተነሣ ከስምንት ዓመታት በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ያምናል። ባመነ በስድስት ዓመቱ (ማለትም ከክርስቶስ ዕርገት አሥራ አራት ዓመታት በኋላ) እየሰበከ ግሪክ አቴና /ATHENS/ ደርሶ ብዙ ፈላስፎችን ወደ ክርስትና ሲያመጣ አንዱ ይህ ቅዱስ ብሩታዎስ ነበር።

ቅዱስ ብሩታዎስ በክርስቶስ አምኖ፣ ተጠምቆ፣ ሐዋርያትን ተከትሏቸው እነርሱም ቅስና ሹመውታል። ጵጵስና እንሹምህ ቢሉት በፊታቸው ተንበርክኮ አልቅሷል። አይገባኝም ማለቱ ነበር።

ታዲያ ቅዱስ ብሩታዎስ ሐዋርያት ስለ ድንግል እመቤታችን ሲጨዋወቱ እየሰማ "መቼ አይቻት።" እያለ በፍቅሯ ይቃጠል ነበር። አንዴ ግን ወሰነ። "እመቤቴን ሳላያት እንቅልፍ አላይም።" ብሎ በሽማግሌ እግሮቹ ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ።

የሚገርመው እርሱ እስራኤል (ጽርሐ ጽዮን) የደረሰው በ፵፱ ዓ.ም ጥር ፳፩ ቀን እመቤታችን ልታርፍ ሰዓታት ሲቀራት ነበር። ቅዱሱ ሽማግሌ እመቤታችንን በአካለ ሥጋ ስላያት በፊቷ እንደ እንቦሳ ዘለለ፤ እየሰገደም አመሰገናት። እመ ብርሃንም በንጹሐት እጆቿ ባረከችውና ዐረፈች።

ይህን ጊዜ ምሥጢር ተገልጦለት ዜማና ቅኔ ያለውን የመጀመሪያውን ውዳሴ ማርያም ዕለቱኑ ደርሶ ለሐዋርያት ሰጣቸው። እነርሱም ከምስጋናው ጣዕም የተነሳ ተደነቁ። ከሐዘናቸውም ተጽናኑ።

ይህ ድርሰት በዘመነ ሰማዕታት በመጥፋቱ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ አምልቶና አጉልቶ ደርሶታል።

ቅዱስ ብሩታዎስ ግን ብዙ ሃገራትን በሐዋርያነት አዳርሶ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ብሩታዎስ ላይ ያሳደረውን የድንግል እናቱን ፍቅር በእኛም ላይ ያሳድርብን።

ሚያዝያ ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ብሩታዎስ ሐዋርያዊ
፪.አባ ዕንባቆም ጻድቅ ሰባኬ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ (ደራሲ፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊና ሊቀ ምኔት)
፫.ቅዱስ አካክሪስ
፬.ቅዱስ ይወራስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዝእትነ ማርያም
፪.አበው ጎርጎርዮሳት
፫.አባ ምዕመነ ድንግል
፬.አባ ዓምደ ሥላሴ
፭.አባ አሮን ሶሪያዊ
፮.አባ መርትያኖስ
፯.አቡነ በጸሎተ ሚካኤል

"ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሠጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና። ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል።
.....ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል። ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድለት እያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።"
(፩ቆሮ ፲፪፥፯-፲፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ስምዖን ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ስምዖን ሰማዕት <3

ቅዱስ ስምዖን የአርማንያ ሰው ቢሆንም ሰማዕትነትን የተቀበለው በሃገረ ፋርስ (በአሁኗ ኢራን አካባቢ) ነው። ፋርስ ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ ተንባላት (መሐመዳውያን) መነሳት ድረስ ባለው ጊዜ ብዙ ሰማዕታት ለክብር በቅተውባታል።

ብዙዎቹ የዚያው (የፋርስ) ዜጐች ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ የተሰውት ከሌላ ሃገር መጥተው ነው። ፋርሳውያን አብዝተው ፀሐይን ያመልኩ ነበርና ክርስቲያኖቹን የሚያሰቃዩት ይህቺውን ፍጡር እያመለኩ እንዲንበረከኩ ነበር።

ቅዱስ ስምዖንም ከፋርስ ግዛቶች በአንዱ ኤጲስ ቆጶስነትን (እረኝነትን) ተሹሞ ነበርና የመከራው ተሳታፊ ሆኗል። በጊዜው ክርስትና እንደ ዛሬው "ሠርግና ምላሽ" አልነበረምና ቅዱስ ስምዖን (እረኛው) እና መቶ ሃምሳ የሚያህሉ ልጆቹ (መንጋው) ስለ ክርስቶስ ፍቅር ብዙ ሆነዋል።
በእምነታቸው ጸንተው በመገኘታቸውም እንዲገደሉ ተወስኖባቸው መቶ ሃምሳ አንዱም ተሰውተዋል።

አምላከ ሰማዕታት በጽናታቸው አጽንቶ ከበረከታቸው ይክፈለን።

ሚያዝያ ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ስምዖን ሰማዕት (አርማንያዊ)
፪.መቶ ሃምሳ ቅዱሳን ሰማዕታት (የስምዖን ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፬.አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

"ልጆች ሆይ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ አሸንፋችሁአቸውማል። በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። እነርሱ ከዓለም ናቸው። ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ። ዓለሙም ይሰማቸዋል። እኛ ከእግዚአብሔር ነን። እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል። ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም።"
(፩ዮሐ ፬፥፬-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ <3

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም። "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው፣ ልዑክ፣ የተላከ፣ የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው። በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፦
የፍጥረታት ሁሉ ጌታ የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ አድጐ፣ ተጠምቆ፣ ጾሞ፣ ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር።

ከተከተሉት የአምስት ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት መረጠ።
እኒህም
፩.ጴጥሮስ የተባለ ስምኦን
፪.እንድርያስ (ወንድሙ)
፫.ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
፬.ዮሐንስ (ወንድሙ)
፭.ፊልጶስ
፮.በርተሎሜዎስ
፯.ቶማስ
፰.ማቴዎስ
፱.ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
፲.ታዴዎስ (ልብድዮስ)
፲፩.ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና
፲፪.ማትያስ (በይሁዳ የተተካ) ናቸው።
(ማቴ. ፲፥፩)

እነዚህን አሥራ ሁለት አርድእቱን ከጠራ በኋላ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር። ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር።

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በኋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው። ለዓለም እረኞች የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ። እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው።
(ማቴ. ፲፥፲፮፣ ዮሐ. ፲፮፥፴፫)
በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው።
(ማቴ. ፲፱፥፳፰)

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ። "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።"
(ማቴ. ፲፰፥፲፰)
"ይቅር ያላችኋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፤ ያላላችኋቸው ግን አይቀርላቸውም።"
(ዮሐ. ፳፥፳፫)

የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. ፲፮፥፲፱)፣ እረኝነትን (ዮሐ. ፳፩፥፲፭) ተቀበሉ። ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው፣ የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. ፭፥፲፫) አላቸው። ወንድሞቹም ተባሉ።
(ዮሐ. ፯፥፭)
ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው።

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ። ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሣኤ ተመለከቱ። እጆቹን እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ።

ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓት ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው ጌታ ሊቀ ጵጵስናን ሹሟቸው ዐረገ።

ለአሥር ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው። በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን ብርሃናውያን ሆኑ። ሰባ አንድ ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ ሦስት ሺህ ነፍሳትን ማረኩ።
(ሐዋ. ፪፥፵፩)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እስራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል። ከዚህ በኋላ ግን እንደ ትውፊቱ ዓለምን በእጣ ለአሥራ ሁለት ተካፈሏት።

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው። እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ።

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ፣ ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ። በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ። በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ፣ ለምጻሞችን አነጹ፣ እውራንን አበሩ፣ አንካሶችን አረቱ፣ ጐባጦችን አቀኑ፣ ሙታንንም አስነሱ። እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ።

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ፣ ቆዳቸው ተገፈፈ፣ በምጣድ ተጠበሱ፣ ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ። ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ። ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና፤ ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን። "አባቶቻችን፣ መምህሮቻችን፣ ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን።

በዚህች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ ሰማዕት ሆኗል። ቅዱሱ ሐዋርያ አባቱ ዘብዴዎስ እናቱ ማርያም ባውፍልያ ትንሽ ወንድሙ ደግሞ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይባላል።

ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ዓሣ አጥማጅነቱን ትቶ ከጌታችን እግር ተምሮ በዓለም ወንጌልን አስፋፍቷል።
(ማር. ፩፥፲፱) ከሌሎቹ ሐዋርያት በተለየም የእንስሳትን ቋንቋ ያውቅ ነበር።

በመጽሐፍ ቅዱስ በሄሮድስ መገደሉ (ሰማዕትነቱ) የተነገረለት ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ብቸኛው እርሱ ነው። ሰማዕት የሆነውም በ፵፬ ዓ.ም ማለትም ከጌታ ዕርገት አሥር ዓመታት በኋላ ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ሳይበተኑ ነው።
(ሐዋ. ፲፪፥፩)

እግዚአብሔር ከቅዱስ ያዕቆብና ከቅድስት ቤቱ በረከት አይለየን።

ሚያዝያ ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ ወልደ ዘብዴዎስ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
፫.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬.አባ ገሪማ ዘመደራ
፭.አባ ጰላሞን ፈላሢ
፮.አባ ለትጹን የዋህ

"በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው። የቂጣ በዓልም ወራት ነበረ።"
(ሐዋ ፲፪፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"መለኮት በሥጋ አካል በመቃብር ሳለ የሥጋ ሕይወት በምትሆን በነፍስ አካል ወደ ሲኦል ወረደ፤ እንደዚህ ባለ ተዋሕዶ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ከትንሣኤ በኋላ አይያዝም፤ አይዳሰስም፡፡ በዝግ ቤት ገብቷልና፡፡ ነገር ግን ምትሐት እንዳይሉት ቶማስ ዳሠሠው፡፡ የተባለውን ከፈጸመ በኋላ ቶማስ አመነበት።"
(ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይማኖተ አበው ፶፮፥፴፯-፴፰)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ነቢይና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ <3

ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል፦ "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ።" ይላቸዋል።
(ሉቃ. ፩፥፮)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!

እነዚህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና የዘካርያስ ደግሞ መቶ ደርሶ ነበር።
ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው።
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች።

በስድስተኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ ሰኔ ፴ ቀን ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል።

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእስራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሄሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕፃን አለና እርሱንም ግደል።" አሉት።

እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል። አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለሦስት (አምስት) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ አምስት (ሰባት) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት።

ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው። እርሷም ስደት ላይ ነበረችና። ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው። ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው። ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ።" አላት። ባርካው አጽናንታውም ተለያዩ።

ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ። ለሃያ አምስት (ሃያ ሦስት) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም። ይህችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም።

ከዚህ በኋላ ሠላሳ ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው፦ "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ።" አለው። ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና።
(ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩)
አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ።" ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና።
(ሉቃ. ፩፥፸፮)

ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ። ያዩት ሁሉ ፈሩት፤ አከበሩት። ቁመቱ ቀጥ ያለ፣ ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ፣ ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ፣ መልኩ የተሟላ፣ ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና።

ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ። ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው። በዚህ አገልግሎት ለስድስት ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ፤ የሚገባበትም ጠፋው።
"እንቢ ጌታዬ! አንተ አጥምቀኝ?" አለው። ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው፤ አጠመቀው። በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል።

ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሄሮድስን ገሰጸው፤ ንጉሡም ተቀይሞ ለሰባት ቀናት አሠረው። ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሄሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው። እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት። አበው "እምሔሶ ለሄሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሄሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር።" ይላሉ። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል።
(ማቴ. ፫፥፩ ፣ ማር. ፮፥፲፬ ፣ ሉቃ. ፫፥፩ ፣ ዮሐ. ፩፥፮)

ርጉም ሄሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች። ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት።

ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ሥልጣን ሰጥቶ አሰናበታት። በመላው ዓለም ለአሥራ አምስት ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዐርፋለች።

"አስማተ ዮሐንስ መጥምቅ - የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች"
፩.ነቢይ
፪.ሐዋርያ
፫.ሰማዕት
፬.ጻድቅ
፭.ካህን
፮.ባሕታዊ (ገዳማዊ)
፯.መጥምቀ መለኮት
፰.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
፱.ድንግል
፲.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
፲፩.ቃለ ዓዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
፲፪.መምህር ወመገሥጽ
፲፫.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

ጌታችን መድኃኔ ዓለም ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ብሎ ይቅር ይበለን። ጸጋውን፣ በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን።

ሚያዝያ ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት (ጸዐተ ነፍሱ)
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ (ከሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት)
፫.ቅዱስ አጋቦስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
፬.ቅድስት እለእስክንድርያ ሰማዕት
፭.አቡነ አቢብ ጻድቅ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፫.ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ
፬.ቅድስት እንባ መሪና
፭.ቅድስት ክርስጢና

"ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ።.....
ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን።.....
እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም።.....
ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ። ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ  ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።"
(ማቴ ፲፩፥፯-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእናቶቻችን ቅዱሳት አንስት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳት አንስት <3

ከትንሣኤ ሳምንት ይህች ዕለት "ቅዱሳት አንስት" (የተቀደሱ ሴቶች) ተብላ ትጠራለች።

በወቅቱ በኢየሩሳሌምና ዙሪያዋ ከተከተሉት ሴቶች ጌታችን ሰላሳ ስድስቱን መርጧል። እነዚህ እናቶች ከዋለበት ውለው ካደረበት አድረው የቃሉን ትምህርት ሰምተዋል። የእጁንም ተአምራት አይተዋል። ፈጽመውም አገልግለውታል።

መጽሐፍ "አንስተ ገሊላ ኩሎን።
አዋልዲሃ ለጽዮን።
አስቆቀዋሁ ለመድኅን።
ከመ ዖፈ መንጢጥ እንዘ ይሤጽራ ገጾን።" ይላልና በዕለተ ዓርብ ፊታቸውን እየነጩ፣ ደረታቸውን እየደቁ፣ እንባቸውም እንደ ጐርፍ እየፈሰሰ አብረውት ውለዋል።

ጌታም ፍጹም ፍቅራቸውን ተመልክቷልና ከሁሉ አስቀድሞ ትንሣኤውን ለእነርሱ ገለጠላቸው። እነርሱም ትንሣኤውን በመፋጠን አብሥረዋል። በዚህም ምክንያት ይህች ዕለት "ቅዱሳት አንስት" ተብላ ትከበራለች።

አምላካችን በፍቅርና በቅድስና ጌጥ ካጌጡ እናቶቻችን በረከትን ያድለን።

"መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፦ 'እናንተስ አትፍሩ። የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና። እንደተናገረ ተነስቷልና በዚህ የለም። የተኛበትን ሥፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሒዱና ከሙታን ተነሣ፤ እነሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል። በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው።'
.....እነሆም ኢየሱስ አገኛቸውና ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት።"
(ማቴ ፳፰፥፭-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፤ ሙታንንም አስነሣ፡፡ እንደ ተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደ ዘበቱበት፣ እንደ ሰደቡት እንዲሁ በሰማይ ያሉ ሁሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፡፡ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ።"
(ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ሃይማኖተ አበው ፯፥፳፰-፴፩)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቃንና ሰማዕታት አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ <3

እነዚህ ሁለት ቅዱሳን የደብረ ኮራሳኑ ጻድቅና ኮከብ የቅዱስ ሜልዮስ ደቀ መዛሙርት ናቸው።
የቅዱስ ሜልዮስ ነገርስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ቅዱስ ሜልዮስ ልጅነቱን በመንፈሳዊ ትምህርት ያሳለፈ በጉብዝናው ወራት ፈጣሪውን ያሰበ ደግ ክርስቲያን ነው። ይህችን ዓለም ከነ ክፋቷ ንቆ ኮራሳት ወደሚባል በርሃ ሔዶ በተራራውና በደኑ ውስጥ በጾምና በጸሎት በትሕርምትም ለበርካታ ዓመታት ተጋድሏል።

በእነዚህ የብሕትውና ዘመናቱ ልብሱን ፀሐይና ብርድ ቆራርጦ ስለ ጨረሳቸው ፈጣሪው ጸጉርን አልብሶታል። የአባ ሜልዮስ ጸጉሩ እስከ እግሩ ጽሕሙ እስከ ጉልበቱ ነበር።

እድሜው ገፍቶ ሲያረጅ እንዲያገለግሉት እግዚአብሔር ሁለት ወጣት ምስጉን ክርስቲያኖችን ላከለት። እነርሱም አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ ይባላሉ። ሁለቱ ቅዱሳን አምላካቸውን እግዚአብሔርንና አባታቸው ቅዱስ ሜልዮስን በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል።

ከቆይታ በኋላ ግን በአካባቢው የነበሩ ጣዖት አምላኪዎች አራዊት እናጠምዳለን ብለው በዘረጉት መረብ ቅዱስ ሜልዮስን ያዙት። ክርስቲያን መሆኑን ሲያውቁ "ለፀሐይ ስገድ።" ብለው ደበደቡት።

ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው መጥተው አባታቸውን በመከራ መሰሉት። ክርስቶስን አንክድም ስላሉ ሁለቱንም በሰይፍ አንገታቸውን መቷቸው። ቅዱስ ሜልዮስን ግን ለአሥራ አምስት ቀናት ካሰቃዩት በኋላ በቀስት በተደጋጋሚ ወግተው ገድለውታል። ጻድቅና ሰማዕት ቅዱስ ሜልዮስ ብዙ ተአምራትን አድርጓል።

ገዳዮች ግን ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ የሜዳ አህያ ሊያድኑ የወረወሩትን ቀስት የእግዚአብሔር መልአክ ወደእነርሱ መልሶባቸው ልብ ልባቸውን ተወግተው ሙተዋል።

ይህች ቀን ቅዱሳን አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ ሰማዕትነትን የተቀበሉባት ናት።

ቸር አምላክ ከቅዱሱ ሜልዮስና ከደቀ መዛሙርቱ በረከትን ያካፍለን።

ሚያዝያ ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩. አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ (ሰማዕታት)
፪.ቅድስት ዲዮኒስ ዲያቆናዊት (የሐዋርያት ተከታይ የነበረች)
፫.ቅዱስ መናድሌዎስ
፬.አባ አኮላቲሞስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬.ቅዱስ አስከናፍር
፭.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን።' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ ፰፥፴፭-፴፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዕለተ አዳም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ዕለተ አዳም <3

ከትንሣኤ በኋላ ያሉት ሰባቱ ዕለታት ስያሜ እንዳላቸው ሰኞ ማዕዶት፣ ማክሰኞ ቶማስ (አብርሃም)፣ ረቡዕ ደግሞ አልዓዛር እንደሚባሉ ተመልክተናል።

ሐሙስ ደግሞ አዳም (የአዳም ሐሙስ) በመባል ይታወቃል። በዚህች ዕለት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ለማዳን መጸነሱ፣ መወለዱ፣ መሰቀሉ፣ መነሣቱና ማረጉ ይነገራል። በዕለቱ ሕፃናቱ "ስለ አዳም" የሚል ባሕላዊ ዜማ እያዜሙ በዓሉን ያዘክራሉ።

አባታችን አዳም የመጀመሪያው ፍጥረት (በኩረ ፍጥረት) ነው።
አባታችን አዳም፦
በኩረ ነቢያት፣
በኩረ ካህናት፣
በኩረ ነገሥትም ነው።

በእርሱ ስሕተት ዓለም ወደ መከራ ቢገባም ወልድን ከዙፋኑ የሳበው የአዳም ንስሐና ፍቅር ነው። አባታችን ለመቶ ዓመታት የንስሐ ለቅሶን አልቅሷል። ስለዚህ አባታችን አዳም ቅዱስ ነው። ከሌሎቹ ቅዱሳን ቢበልጥ እንጂ አያንስም።

"በክርስቶስ በሰማያዊ ሥፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ። ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።"
(ኤፌ ፩፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ክርስቶስ የሙታን በኵር እንደ ምን ተባለ? እነሆ በናይን ያለች የድሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዓዛርን በሞተ በአራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፤ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታንን አስነሣ። አንዱን ሳይቀበር፤ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ሆነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኵር ነው፡፡ እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፡፡ 'ዳግመኛም ሞት አያገኘውም።' ተብሎ እንደ ተጻፈ።"
(ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይማኖተ አበው ፶፯፥፫-፮)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሰማዕታተ ኢትዮጵያ <3

አመ ዐሡሩ ወአሚሩ ለሚያዝያ በዛቲ ዕለት አዕረፉ ሰማዕታተ ኢትዮጵያ። በረከቶሙ የሃሉ ምስሌነ ለዐለመ ዐለም አሜን፡፡
ከመዝ ኮነ በውስተ ሀገረ ሊብያ በዕሥራ ምዕት ወሰብዐቱ ዐመተ ምሕረት፡፡ በአሜሃ ዘመን ተንሥኡ ተንባላት እለ ስሞሙ አይሲስ በውስተ ሀገረ ኢራቅ ወሶርያ ወሊብያ ወየመን፡፡ አሐዙ ይቅትሉ ሰብአ ዘረከቡ ወፈድፋደሰ እለ ኮኑ ክርስቲያነ በእምነቶሙ፡፡
ብዙሓን ክርስቲያን ተመትሩ አርእስቲሆሙ በአይሲስ ወተወክፉ አክሊለ ስምዕ እምእላ ሀገራት፡፡ በዝ ዘመን ውእቱ ዘረከቦሙ አይሲስ ለሰብአ ኢትዮጵያ በውስተ ሀገረ ሊብያ እንዘ የሐውሩ ኀበ ሀገረ ኢጣልያ በእንተ መፍቅደ ልቦሙ፡፡ እሉ ከሀድያን ውሉደ ሰይጣን ወአራዊተ ገዳም አሐዝዎሙ ወአዘዝዎሙ ወአፍርሕዎሙ ከመ ይክሀዱ ስሞ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡፡
ወእምዝ ዘበጥዎሙ በዘዚአሁ ዝብጠታተ በእንተ ዘኮኑ ክርስቲያነ ርእዮሙ ማዕተበ ክሣዶሙ፡፡ ውእቶሙሰ አበዩ ይእዜኒ ክሂደ ሃይማኖቶሙ እመኒ አመከርዎሙ በረሐብ ወጽምዕ ወበካልኣን ኵነኔያት፡፡ ሶበ አበዩ ክሂደ ወሰድዎሙ ኀበ ምድረ በድው ኀበ አልቦ እክል ወማይ ከመ ይእመኑ እምጽንዐ ረሐብ ወጽምዕ፡፡
ወእምዝ ጠየቅዎሙ ከመ ይብትኩ ማዕተበ ክሣዶሙ ወይክሀዱ ስሞ ለእግዚአብሔር አምላኮሙ፡፡ እሉሰ ሰማዕታት ይእዜኒ አበዩ ክሂደ ስሞ ለፈጣሪሆሙ፡፡ አዲ ይቤልዎ ለአይሲስ "ኦ አይሲስ ለእመ ክህልከ ቀቲሎታ ለሥጋነ ኢትክል ቀቲሎታ ለነፍስነ፡፡ ኢንፈርሕሂ ወኢንደነግጽ እምብልሐ ሰይፍከ እስመ አቅዲሙ ነገረነ አምላክነ እንዘ ይብል ኢትፍርሕዎሙ ለእለ ይቀትሉ ሥጋክሙ ወለነፍስክሙሰ ኢይክሉ ቀቲሎታ፡፡"
አዲ ይቤለነ በውስተ ወንጌሉ ቅዱስ እስመ ኵሉ ዘከቀተለክሙ ይመስሎ ከመ ዘመሥዋዕተ ያበውእ፡፡ ይእዜኒ አንተ ላእኩ ለዲያብሎስ ፈጽም በላዕሌነ መልእክተከ ሰይጣናዌ ወአብእ መሥዋዕተከ ርኩሰ ለእምላክከ ሰይጣናዊ፡፡ ንህነኒ ናበውእ ክሣደነ ንጹሐ ለእምላክነ ዘፈጠረነ እስመ ነአምር ዘከመ ያነሥአነ በትንሣኤሁ ቅድስት አመ ዳግም ምጽአቱ፡፡
አሲስኒ አላዊ መተሮሙ አርእስቲሆሙ በሰይፍ ወኮኑ ሰማዕተ በከመ ዛቲ ዕለት፡፡ ወእምዝ ተሀውከት ኵላ ኢትዮጵያ ወኵላ ዐለም እስመ ትርእየ ትእይንተ ጥብሐቶሙ ለሰማዕታት በመስኮተ ትእይንት፡፡ ኵሎሙ ሰብአ ኢትዮጵያ አስቆቀዉ ወበከዩ ብካየ መሪረ እንዘ ይገብሩ ሰላማዌ ትእይንተ በበአዕዋዲሁ ወበበፍኖቱ፡፡
ወይብሉ በበቃሎሙ "አይሲስ አይሲስ እንተ ትቀትሎሙ ለሰማዕታት: ወታውሕዝ ደመ ንጹሓን በበፍናዊሁ ከመ ደመ አክልብት: ይደልወከ ትቁም ውስተ ዐውደ ፍትሕ ሰማያዊ፡፡"
በዝንቱ ዘመን ቈስለ ልቡ ለህዝብ በሐዘነ ሥጋ እስከነ ይብል "ፍትሐ ጽድቅ ዘዐርገት ውስተ ሰማይ ከመ ትንበር ምስለ ዘፈጠራ እግዚአብሔር እስመ ኢረከበት ውስተ ዛቲ ምድር ኀበ ትነብር ወኀበሂ ታጸልል፡፡ ናሁ ይጸርሕ ደሞሙ ለሰማዕታት ቅድመ ገጹ ለኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ይረድ ፍትሐ ርትዕ ዲበ ምድር ወይሠረው አሲስ እምውስተ ገጻ ለምድር፡፡"
በረከቶሙ: ወጽንዐ ገድሎሙ ለእሉ ሰማዕታት ይሕድር ላዕሌነ ለዐለመ ዐለም አሜን፡፡

ሰላም ለክሙ በቃለ ማሕሌት ወእንዚራ፡፡
ምስለ ሰማዕታት ዘግብጽ መከራቲክሙ ዘሐብራ፡፡
ቅዱሳን ሰማዕታት ዘኦርቶዶሳዊት ሐራ፡፡
እፎ ክህልክሙ ተዐግሦ ጽኑዕ መከራ፡፡
እስከ ክሳውዲክሙ በአሲስ ተመትራ፡፡
(ኢያዕመርኩ ከመ መኑ ጸሐፎ)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"በታወቀች በተረዳች በሦስተኛይቱ ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገባ፡፡ የተወጋውን ጎኑን፣ የተቸነከረውን እጁን፣ እግሩን አሳያቸው፡፡ በዓለመ ነፍስ የሆነውን እያስተማራቸው ዐርባ ቀን ኖረ።"
(ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት ፬፥፳፭-፳፯)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባ ይስሐቅ ጻድቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ይስሐቅ ጻድቅ <3

ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆኑ የነበሩት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። በጊዜው ዝነኛ ከነበሩት ከታላቁ አባ ዕብሎ (ቅዱስ ዕብሎይ) ተምረዋል። መማር ብቻ ሳይሆንም ለሃያ አምስት ዓመታት ያለ መታከት በተልዕኮ አገልግለዋል።

በእነዚህ ጊዜያትም ትሕርምትን፣ ተጋድሎን፣ ትምህርተ ቅድስናንና ሌሎች አስፈላጊ መንፈሳዊ ስንቆችን ሰንቀዋል። በመታዘዛቸው በምድር አበውን በሰማይ እግዚአብሔርን አስደስተዋል። በዚህም ከእግዚአብሔር ጸጋውን ከአበው ምርቃትን አትርፈዋል።

ጊዜው ደርሶም ታላቁ ዕብሎ ሲያርፉ አባ ይስሐቅ በዓት ለይተው ደንበኛውን ተጋድሎ ጀምረዋል። አምላካቸውን ለማስደሰትና በቅድስና ለመዝለቅም የአርምሞ ሰው ሁነዋል። ለሚገባው ነገር ካልሆነ በቀር አያወሩም፤ ምላሽም አይሰጡም።
"ለምን?" ሲባሉ
፩."ለሁሉም ጊዜና ቦታ አለው።"
፪."ሰው በከንቱ በማውራቱ ከጸጋ እግዚአብሔር ይርቃል።" ይሉ ነበር።

አባ ይስሐቅ የክርስቶስ መድኃኒታችንን ሕማማት ለማዘከር ሁሌ ያነቡ (ያለቅሱ) ነበር። ቅዳሴ ሲያስቀድሱ እጃቸው የኋሊት ታስሮ ነበር። ቅዱሱ ሰው ለአዝማናት እንዲህ ተመላልሰው በመልካም ዕርግና ያረፉት በዚህች ቀን ነው።

አምላከ ቅዱሳን ከበረከታቸው አይለየን።

ሚያዝያ ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ይስሐቅ ገዳማዊ (የታላቁ ዕብሎይ ደቀ መዝሙር)
፪.አባ ገብርኤል ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
፬.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፮.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፯.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

"የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ
ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ።
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።"
(ይሁዳ ፩፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዕለተ ማዕዶት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ማዕዶት <3

ማዕዶት ማለት (ዐደወ ተሻገረ) ከሚል የግእዝ ግስ የተወረሰ ሲሆን በጥሬው "መሻገር" ማለት ነው። ይህም በደመ ክርስቶስ ተቀድሰን በትንሣኤውም ድኅነት ተደርጐልን መከራን መርገምን የኃጢአትን ባሕር አንድም ባሕረ እሳትን መሻገራችንን ያመለክታል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ
ከባርነት ወደ ነጻነት፣
ከጨለማ ወደ ብርሃን፣
ከሞት ወደ ሕይወት፣
ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣
ከሲዖል ወደ ገነት፣
ከገሐነመ እሳት ወደ መንግሥተ ሰማያት
አዳምንና እኛን ልጆቹን አሸጋግሮናል።

አባታችን አዳምና ልጆቹ ከሲዖል የወጡት በዕለተ ዓርብ በሠርክ ቢሆንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዕለት እንዲታሰብ ታዝዛለች።

ጌታችን ምርኮን ማርኮ ጥጦስ መንገድ ጠራጊ ሆኖለት ወደ ገነት ሲያስገባቸው ለድንግል ማርያም አሳይቷታል። እመ አምላክም በፍጹም ልቧ ደስ ተሰኝታለች። አዳምና ልጆቹ እመቤታችንን ከላይ ሆነው እጅ ነስተዋታል። እርሷ የድኅነታቸው ምክንያት ናትና።

አማናዊው ብርሃን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ጨለማችንን በምሕረቱ ያብራልን።

"ክርስቶስም እኮ ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ ሞቶአል። ኃጢአት የሌለበት ክርስቶስ ጻድቁ ስለ እኛ ሞተ። ስለ ኃጢአታችን እኛን ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ።
በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ነው። ነፍሳቸው ታስራ ወደ ነበረችበት ሔደ። ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ነጻነትን ሰበከላቸው።"
(፩ጴጥ ፫፥፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳት ደናግል ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳት ደናግል <3

ቅዱሳት ደናግሉ አጋሊዝ (አጋሊስ)፣ ኢራኒና ሱስንያ ይባላሉ። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ተሰሎንቄ የምትባል ሃገር ውስጥ ይኖሩ ነበር። ሦስቱም እጅግ ቆንጆዎችና ከብዙ ወንዶች ዓይን የሚገባ መልክ ቢኖራቸውም የእነርሱ ምርጫ ግን ሰማያዊ ሙሽርነት ነበርና በጾምና በጸሎት ተወሰኑ።

ለብዙ ዓመታትም ደናግሉ በሚኖሩበት ደብር ውስጥ በቅድስና ኑረዋል። ከቆይታ በኋላ ያ የመከራ ዘመን (ዘመነ ሰማዕታት) ሲመጣ ለጊዜውም ቢሆን ወደ በርሃ ሸሽተው ተቀመጡ።

ያሉበትን ቦታ የምታውቅ አንዲት ደግ ባልቴት እየሔደች ትጎበኛቸው በእጃቸው የሚሠሯቸውን የተለያዩ እቃዎችንም እየሸጠች እኩሉን በስማቸው መጽውታ በተረፈው ለራት የሚሆን ደረቅ ቂጣ ትገዛላቸው ነበር።

አንድ ቀን ግን አንድ አረማዊ ሰው ተከትሏት መጥቶ በማየቱ ሦስቱንም ደናግል ወደ ከሐዲው ንጉሥ አቀረባቸው። ንጉሡ ሃይማኖታቸውን ቢክዱ የሃብትና የሥልጣን ተስፋ እንዳላቸው ነገራቸው። ደናግሉ ግን በፍቅረ ክርስቶስ በመጽናታቸው ከብዙ ስቃይ በኋላ በዚህች ቀን አስገድሏቸዋል።

የጌታችን በጐ ምሕረቱ በሁላችን ትደርብን። ከደናግሉ በረከትን ያሳትፈን።

ሚያዝያ ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳት ደናግል አጋሊዝ፣ ኢራኒና ሱስንያ
፪.መቶ ሃምሳ ቅዱሳን ሰማዕታት (ፋርስ - ኢራን ውስጥ የተሰየፉ)
፫.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፫.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፬.አቡነ ኪሮስ
፭.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን።' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ ፰፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ በብኑዳ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሰማዕቱ በብኑዳ <3

ቅዱስ በብኑዳ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ በምድረ ግብጽ ተባሕትዎን መርጦ የሚኖር ገዳማዊ አባት ነው። በበርሃ በጾምና በጸሎት ተወስኖ ለእግዚአብሔር የምስጋናን መስዋዕት እየሠዋ አገልግሏል።

በዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖች በግፍ ሲገደሉ ቅዱሱ ሰው በበርሃ ውስጥ ነበር። አንድ ቀን የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ሰማዕት እንዲሆን መከረው። እርሱም ነጭ በነጭ ለብሶ አምሮበት ወደ ንጉሡ ሔደ። በፊቱም ቀርቦ በክርስቶስ ስም ታመነ። ብዙ ጸዋትወ መከራም ተቀበለ።

ንጉሡ (መኮንኑ) "አመጣጥህ ወደ ሞት ሳለ ምነው እንዲህ እንደ ሠርገኛ ማጌጥህ?" ቢለው "እኛ ክርስቲያኖች ትልቁ ሠርጋችን ሞታችን ነው። ልንሔድ ከክርስቶስም ጋር ልንኖር እንናፍቃለንና።" ብሎታል።

ቅዱስ በብኑዳ ብዙ ተሰቃይቶ ተአምራትን ሰርቶ በዚህች ቀን ተሰይፏል። የጽድቅን አክሊል ከሰማዕትነት ጋር ደርቦ አግኝቷል።

ቸሩ አምላክ ከሰማዕቱ በረከትን ያካፍለን።

ሚያዝያ ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ በብኑዳ (ሰማዕት ወጻድቅ)
፪.ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሚስቱና አሥራ ሁለት ልጆቹ ሰማዕታት (ከቅዱስ በብኑዳ ጋር የተገደሉ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፫.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፬.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፭.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፮.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

"በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ፤ አትናወጡም። ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ
ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን።"
(፩ጴጥ ፫፥፲፫-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት አባ ጴጥሮስ ዓመታዊ
የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጻድቅና ሰማዕት አባ ጴጥሮስ <3

ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው። ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል። ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው።
ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል። የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው።
"አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ።
ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው።

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ!
በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ። ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም።
እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ።" ብሎናልና።
(ማቴ. ፭፥፵፬)
ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል።

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል። የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና።

ቅዱስ አባ ጴጥሮስም ከዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች አንዱ ነው። በዚያ የመከራ ዘመን (ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ግብጽና ሶርያ በብዙ መከራ ውስጥ ሳሉ በርካታ ቅዱሳን ተሰውተዋል። በተለይ በግብጽ ደግሞ ብዙ ንጹሐን አበውና ቅዱሳት አንስት መከራውን ታግሠው ለክብር በቅተዋል።

ከእነዚሁ አንዱ የሆነው አባ ጴጥሮስ ገና ከልጅነቱ ጣዕመ ክርስትናን የተማረው ከአሳዳጊው (ከአክስቱ) ነበር። በፍፁም ልቡ የሚወደው ወንድም እና ባልንጀራም ነበረው። ስሙ ደግሞ አባ ብሶይ ይሰኛል። ሁለቱም በበጎ ምግባር ተኮትኩተው ዓለምንም ንቀው በርሃ ገብተው በጾም በጸሎት ተወስነው ብዙ ጊዜ ኑረዋል።

በመከራው ዘመን ደግሞ ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ተከሰው ታስረዋል። ተገርፈው ተደብድበዋል። ጭንቅ ስቃይንም በትእግስት አሳልፈዋል። በፍጻሜውም አባ ጴጥሮስ በዚህች ቀን ተሰውቶ ለክብር አክሊል በቅቷል። ወዳጁና ወንድሙ ቅዱስ ብሶይም በክብር ገንዞ ቀብሮታል።

አምላከ ሰማዕታት ከጸናች ገድላቸው፣ ከበዛች ትእግስታቸው፣ ከፍጹም በረከታቸው ያሳትፈን።

ሚያዝያ ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ጴጥሮስ ሰማዕት
፪.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት
፫.ሰማዕታተ ጠርሴስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
፫.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

"በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሠር አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ።
.....በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።
.....የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።"
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ አንቲቦስ ሐዋርያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አንቲቦስ <3

በዚህች ቀን ታላቁ ሐዋርያና ሰማዕት ቅዱስ አንቲቦስ ይታሰባል። ቅዱሱ በአርማ በምትባል ሐገር በእረኝነት (ጵጵስና) ያገለገለ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ነው።

ቅዱሱ ስለ ክርስቶስ መንጋ ብዙ መከራን ተቀብሏል። በእሥር ቤት ሳለም ከቅዱስ ዮሐንስ ነባቤ መለኮት (ወንጌላዊ) ክታብ (መልእክት) ደርሶታል። በክታቡም ከሐዋርያትና ሰማዕታት መቆጠሩን ነግሮታል። ጊዜው አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን ክታቧ ከእኛ አልደረሰችም።

ከቅዱስ ዮሐንስ እግር ቁጭ ብሎ በመማሩ እንደ መምህሩ የንጽሕና ሰው ነበር። ከብዙ ዓመታት አገልግሎት በኋላ ስለ ፍቅረ ክርስቶስ በዚህች ቀን በሰማዕትነት አልፏል።

በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ደግሞ የዚህ ቅዱስ ስም መጠቀሱን ምስራቅ ኦርቶዶክሶች ያምናሉ። በዮሐንስ ራዕይ ፪፥፲፪ ላይ የእኛው (ግዕዙ) "ጻድቅየ መሃይምን" ሲለው የግሪኩ ግን በቀጥታ በስሙ "አንቲጳስ (አንቲቦስ) ብሎ ይጠራዋል። እርሱም በታናሽ እስያ ከነበሩት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ (የጴርጋሞን) አለቃ የነበረ ሲሆን ሰማዕት መሆኑም በዚሁ ምዕራፍ ላይ ተጠቅሷል።

"በጴርጋሞንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል። 'የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ። ሰይጣንም በሚኖርበት በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም። ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ። እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ። እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ። በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ
ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ። ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ። በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል።' "
(ራእይ ፪፥፲፪-፲፯)

አምላካችን ከቅዱስ አንቲቦስ በረከትን ያሳትፈን።

ሚያዝያ ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አንቲቦስ ዘሃገረ በአርማ (ሐዋርያዊ ጳጳስና ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ሳባ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
፬.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፯.አባ ዳንኤል ጻድቅ

"የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ። የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ። ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም። በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።"
(ዕብ ፲፫፥፯-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዳግሚያ ትንሣኤ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይድረሰውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በጉባኤ ሦስት ጊዜ ተገልጦላቸዋል።
፩.በዕለተ ትንሣኤ ምሽት በፍርሃት ሳሉ
፪.ያላመነ ቶማስን ለማሳመን በተነሣ በስምንተኛው ቀን (ማለትም ዛሬ)
፫.ከተነሣ ከሃያ ሦስት ቀናት በኋላ በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ላይ ነው።

ጌታ አርባውን ቀን ለአንዱም ለሁለቱም በግል ይገለጥላቸው ነበር። እመቤታችንን ግን ፈጽሞ አይለያትም ነበር።

ጌታችን ከተነሣ በኋላ ለሳምንት ተለይቷቸው ስለ ነበር በቤተ ክርስቲያን ውዳሴ ማርያም እንጂ መልክአ ኢየሱስ በማኅበር አይደገምም።

በዚህች ዕለት ደቀ መዛሙርቱ በጽርሐ ጽዮን ሳሉ ጌታችን "ሰላም ለእናንተ ይሁን።" ብሏቸዋል። ቶማስንም "ና ዳስሰኝ።" ብሎታል። ሐዋርያው እጁን ከተወጋ ጐኑ ላይ ቢያሳርፍ በመቃጠሉ "ጌታዬ አምላኬም" ሲል ጮሆ ምሥጢረ ተዋሕዶውን መስክሯል።

ጌታም ቶማስን "እስመ ርኢከኒሁ አመንከኒ - ስላየኸኝ አመንከኝ!
ብጹዐንሰ እለ እንዘ ኢይሬእዩኒ የአምኑኒ - ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብጹዐን (ንዑዳን ክቡራን) ናቸው።" ብሎታል።
(ዮሐ. ፳፥፳፬)

ጌታችን ከትንሣኤው እና ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከትን ያድለን።

"ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ። በመካከላቸውም ቆሞ 'ሰላም ለእናንተ ይሁን።' አላቸው። ከዚያም በኋላ ቶማስን 'ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ። እጅህንም አምጣና በጐኔ አግባው። ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን።' አለው። ቶማስም 'ጌታዬ አምላኬም' ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም 'ስላየኸኝ አምነሃል። ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው።' አለው።"
(ዮሐ ፳፥፳፮-፳፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ነፍሱን ከሥጋው አዋሕዶ በመለኮታዊ ኃይል ተነሣ፡፡ እርሱ ራሱ 'ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ ልሰጥ፣ ሁለተኛም መልሼ ላዋሕዳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።' እንዳለ፡፡ በነጋም ጊዜ ለማርያም መግደላዊት ታያት፤ እጅ ልትነሣው በወደደች ጊዜም 'ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ።' አላት፡፡ ስለዚህም ሥጋዊ አካሉ ከዚያን አስቀድሞ በአብ ቀኝ እንዳልተቀመጠ ዐወቅን።"
(አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ ምሥጢር ዘትንሣኤ ፺፭)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባ መክሲሞስ ሊቀ ጳጳሳት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ መክሲሞስ ሊቀ ጳጳሳት <3

'ጳጳስ' ማለት 'አባት - መሪ - እረኛ' ማለት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ሥልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ ሦስት ናቸው። እነሱም ዲቁና፣ ቅስና፣ ጵጵስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ ዘጠኝ ያህል ክፍሎች አላቸው። ከእነዚህም ከፍተኛው ሥልጣን ጵጵስና ነው።

ጵጵስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው። ሥልጣኑ በምድር 'ሸክም ዕዳ' ሲሆን በሰማይ ግን 'ክብር' ነው። ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ጵጵስናን አይመኝም።

ቅዱስ ጳውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ጵጵስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ።" (፩ጢሞ. ፫፥፩) ማለቱን ይዞ 'ሹሙኝ' ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው። ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል። የከፋው ግን የጳጳሱ ነው።

አንድ ጳጳስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም። ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና። ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው።" (ዮሐ. ፲)
ስለዚህም ክህነት/ጵጵስና ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው።

አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የጵጵስና መናብርትን መሥርተው ትምህርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል። ከእነዚህ መንበረ ጵጵስናዎች አራቱ የበላይ ናቸው። እነዚህም የቅዱስ ጴጥሮሱ የሮም፣ የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ፣ የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ጳውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው።

እነዚህ መናብርት ከክርስቶስ ዕርገት እስከ ፬፻፵፫ (፬፻፶፩) ዓ.ም ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል። ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው።

የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ጳጳሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች፤ ታከብራለች።

በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን። እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና። ከእነዚህም መካከል አንዱ አባ መክሲሞስ ነው።

አባ መክሲሞስ የእስክንድርያ (ግብጽ) አሥራ አምስተኛ ፓትርያርክ ሲሆን በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ለአሥራ አምስት ዓመታት አገልግሏል። ቅዱሱ ከልጅነቱ ጀምሮ ምሥጢረ ሃይማኖትን የተማረ ሲሆን መናኝ ሰው እንደ ነበርም ይነገርለታል።

በደቀ መዝሙርነትም ለአባ ያሮክላ (አሥራ ሦስተኛው ሊቀ ጳጳሳት) እና ለአባ ዲዮናስዮስ (አሥራ አራተኛው ሊቀ ጳጳሳት) በትህትና አገልግሏል። ዲቁናና ቅስና ሹመት ያገኘውም በዚህ ጊዜ ነው።

ፓትርያርክ ሆኖ ከተመረጠ በኋላም ምዕመናንን በአፍም በመጣፍም ብሎ አስተምሯል። በዚህም መንጋውን ከተኩላ የመጠበቅ ተግባርን ከውኗል። በተለይ ደግሞ ዓለማቀፍ መናፍቃን የሆኑትን ማኒንና ሳምሳጢን ተዋግቷል። ትግሉም ተሳክቶ መናፍቃኑ ተወግዘዋል።

ቅዱሱ አባት አባ መክሲሞስ (ማክሲሙስ) ከዚህም የሚበልጥ ብዙ በጐ ሥራ ሠርቶ በበጐ ዕረፍት በዚህች ቀን ዐርፏል።

አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ብሎ ለመንጋው የሚራራ እረኛን ይስጠን። ከቅዱሱ በረከትንም ይክፈለን።

ሚያዝያ ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ መክሲሞስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

"ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።"
(ሐዋ ፳፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዕለተ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን (ለነፍሳተ ብሉይ) ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

ከትንሣኤ ሳምንት ቀናት ይህች ዕለት "ቤተ ክርስቲያን" አንድም "ነፍሳት" በመባል ትታወቃለች።

<3 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድንገት የተመሠረተች ሳትሆን ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና የታሠበች በዓለመ መላእክት የተወጠነች ናት። በአማን ጐልታ ግዘፍ ነስታ የተመሠረተችው ግን በደመ ክርስቶስ ተቀድሳ በትንሣኤው ከብራ ንጽሕትና ጽሪት ባደረጋት ጊዜ ነው።

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ባይነሳ ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ሕልውና አይኖራትም ነበርና ይህች ዕለት "ቤተ ክርስቲያን" ተብላ ትከበራለች።

<3 ነፍሳት <3

በብሉይ ኪዳን የነበሩና ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በሲዖል የተጋዙ ሰዎችን ያመለክታል። እነርሱም ከአባታችን አዳም ጀምሮ በዓመተ ኩነኔ የነበሩ ሰዎች ሲሆኑ ደመ ክርስቶስ ቀድሷቸው የትንሣኤው ብርሃን ደርሷቸው ወደ ገነት ስለ ገቡ በዚሁ ቀን ይታሠባሉ።

እግዚአብሔር ከአባቶች ነፍስና ከቅድስት ቤቱ በረከት አይለየን።

"መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ ተቀበረም። መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነስቷል።
.....ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ። ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና። የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብየ ልጠራ የማይገባኝ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ።"
(፩ቆሮ ፲፭፥፫-፲)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን የከፈተልን፤ ዕፀ ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደው፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፡፡ ፍሬውንም (ሥጋውን፣ ደሙን) ተቀበልን፡፡ አባታችን አዳም ሊደርስበት ወዳልተቻለው፤ በራሱ ስሕተት ተከልክሎበት ወደ ነበረው መዓርግ ደረስን፡፡ ክፉዉንና በጎዉን ከሚያስታውቅ፤ ወደ ጥፋት ከሚወስድ፤ በአዳምና በልጆቹም ላይ ኃጢአት ከመጣበት ከዕፀ በለስ ፊታችንን መለስን።"
(ዝኒ ከማሁ ፴፮፥፴፰-፴፱)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ኤርምያስ <3

ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ከዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስድስት መቶ ዓመት አካባቢ የነበረ ነቢይ ነው። አባቱ ኬልቅዩ ይባላል። ከካህናተ እስራኤል አንዱ ነበር።

እግዚአብሔር ኤርምያስን የጠራው ገና በሕፃንነቱ ነበር። "ከእናትህ ማኅጸን ሳትወጣ መርጬሃለሁ፤ ቀድሼሃለሁ።" ሲልም በገሃድ መስክሮለታል።
(ኤር. ፩፥፭)

ከቅዱሳን ነቢያት እንደ ኤርምያስ የተሰቃየና ያለቀሰ የለም። ከሰባ ዘመናት በላይ ስለ ወገኖቹ አልቅሷልና። ሊቃውንት "ነቢየ ብካይ" (ባለ እንባው ነቢይ) ይሉታል።

ዘመኑ ዘመነ ኃጢአት (ዘመነ ዐጸባ) ነበር። እስራኤላውያን ከመሪዎቻቸው ከነ ሴዴቅያስ ጋር በክፋት ተባብረውም ነበርና ኤርምያስን አልሰሙትም። ይልቁኑ ክፉ ቦታ ውስጥ አስረው አሰቃዩት። እግዚአብሔር ግን በኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ አማካኝነት ከመከራው አዳነው።

የተሰበከላቸውን የንስሐ ጥሪ አልሰሙምና ስልምናሦር የሚባል የአሕዛብ ንጉሥ መጥቶ አሥሩን ነገድ ማርኮ አሦር (ነነዌ) አወረዳቸው። በኋላ ደግሞ በኃይለኝነቱ የታወቀው የባቢሎን ንጉሥ ይማርካቸው ዘንድ ወደ ሁለቱ ነገድ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ኤርምያስ ወደ ከተማዋ ዳር ወጥቶ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቀሰ።

ከቤተ መቅደስ ንዋያት እኩሉን ለምድር አደራ ሰጣትና ሸሸገችው። ነቢዩ የተናገረው አይቀርምና ንጉሡ ናቡከደነጾር እኩሉን ገድሎ እኩሉንም ማርኮ ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ የአሕዛብ መዘባበቻ አድርጐ ባቢሎን አወረዳቸው።

ቅዱስ ኤርምያስን ግን ትሩፋን (ከመከራው የተረፉት) ይዘውት ወደ ግብጽ ወረዱ እንጂ አልተማረከም።

በዚያም ተአምራትን አድርጐ አራዊትን አጥፍቷቸዋል። ትንሽ ቆይቶ ግን እውነተኛ አባት፣ ነቢይ፣ መምህርም ነውና ወደ ሕዝቡ (ወደ ባቢሎን) ወረደ። በዚያም ትንቢትን እየተናገረ ሕዝቡን ከሰባ ዓመታት በኋላ ወደ ሃገራቸው እንደሚመለሱ እያስተማራቸው በባቢሎን ቆይቷል። ያለ በደሉም በመከራቸው ተካፋይ ሆኗል።

ሰባው ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ በኤርምያስ መሪነት እስራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። አሁንም ግን ክፋታቸውን ይተው ዘንድ ፈቃደኞች አልነበሩምና ኤርምያስ ገሠጻቸው።

በዚህ ተበሳጭተው ሊወግሩት ሲሉ ጸጋ በዝቶለት ምሥጢርም ሰፍቶለት ስለ ነገረ ሥጋዌ (ስለ ክርስቶስ የማዳን ሥራ) አምልቶና አጉልቶ ትንቢት ተናገረ። አንዴ ልቡናቸው ታውሮ ኤርምያስ ነው ብለው ድንጋዩን በድንጋይ ሲወግሩት ውለዋል። ዘግይቶ ግን ኤርምያስ ራሱን ገለጠላቸው። ስለ እነርሱ ሲል ሰባ ዘመን ያለቀሰውንና ምትክ የሌለውን አባታቸውን ወግረው ገደሉት።

ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ሃምሳ ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት ጽፏል። ዜና ሕይወቱ ከራሱ የትንቢት መጽሐፍ በተጨማሪ በተረፈ ኤርምያስ፣ በመጽሐፈ ባሮክ፣ በገድለ ኤርምያስ፣ በዜና ብጹዐን፣ በመጽሐፈ ስንክሳርም ተጽፏል።

በዚህች ዕለት ንጉሡ ሴዴቅያስ ቅዱስ ኤርምያስን አስሮት እያለ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ አቤሜሌክ ያስፈታበት (ከረግረግ ያወጣበት) ይታሰባል።

ቸር እግዚአብሔር በኤርምያስ ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት ሕዝቦቿን ከስደትና ከመቅሰፍት ይሰውርልን።

ሚያዝያ ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ
፪.ቅዱስ አቤሜሌክ ኢትዮጵያዊ
፫.አቡነ ሳሙኤል ዘቆየጻ (ኢትዮዽያዊ)
፬.ቅዱስ ባሮክ
፭.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ዘኢየሩሳሌም

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፭.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፮.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
፯.ቅዱስ ድሜጥሮስ

"ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ እንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።"
(ማቴ ፳፫፥፴፯-፴፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅድስት ዕለተ አልዓዛር በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አልዓዛር <3

ከትንሣኤው ሳምንት ይህች ዕለተ ረቡዕ "አልዓዛር" ትባላለች። ጌታችን ከሙታን ስላስነሳው ዕለቷ የሐዋርያው መታሰቢያ ሆናለች።

ቅዱስ አልዓዛር በሃገረ ቢታንያ ከእኅቶቹ ማርያና ማርታ ጋር ይኖር ነበር። ሦስቱም ድንግልናቸውን ጠብቅው ጌታችንን ያገለግሉት ነበርና አልዓዛርን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ማርያና ማርታን ደግሞ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል።

በወንጌል ጌታችን ይወዳቸው እንደ ነበር ተገልጧል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወድ የሚያበላልጥ ሆኖ አይደለም። ይልቁኑ በምሥጢር እነርሱ ተወዳጅ የሚያደርጋቸውን ሥራ ይሠሩ እንደ ነበር ሲነግረን ነው እንጂ።

ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን ጌታችን በነ አልዓዛር ቤት በእንግድነት ይስተናገድ ነበር። በመጨረሻዋ ምሴተ ሐሙስም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለሐዋርያቱ ያቀበላቸው በእነዚህ ቅዱሳን ቤት ውስጥ ነው።

ቅዱስ አልዓዛር በጽኑዕ ታሞ ዐርፏል። ቅዱሳት እኅቶቹ ማርያና ማርታ ከታላቅ ለቅሶ ጋር ዕለቱኑ ቀብረውታል።
(ዮሐ. ፲፩፥፩)
ቸር ጌታችን ክርስቶስ ከአራት ቀናት በኋላ ሊያስነሳው ይመጣል።

ለስም አጠራሩ ስግደት፣ ክብር፣ ጌትነት ይድረሰውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛር ባረፈ በአራተኛው ቀን ወደ ቢታንያ ደረሰ። ማርታ ቀድማ ወጥታ ከእንባ ጋር ተቀበለችው። "አዳም ወዴት ነህ?" ያለ የአዳም ፈጣሪ "አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት?" አለ።
(ዘፍ. ፫፥፲፯)
ቸርነቱ ባሕርዩ ያራራዋልና ማርያም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አብሮ አለቀሰ።

ከዚያም በባሕርይ ሥልጣኑ "አልዓዛር! አልዓዛር!" ብሎ አልዓዛርን አስነሳው። ይህች ተአምርም በአይሁድ ዘንድ ግርምት ሆነች። ለጌታም የሞት ምክንያት አደረጓት። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ እንዲህ ታስተምራለች።
(ዮሐ. ፲፩፥፩ - ፍጻሜው)

ቅዱስ አልዓዛር ጌታችን ካስነሳው በኋላ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ (ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ነውና።) ለአርባ ዓመታት ወንጌልን አስተምሮ በ፸፬ ዓ.ም አካባቢ ቆጵሮስ ውስጥ ዐርፏል።

የጌታችን ቸርነቱ የአልዓዛር በረከቱ ይድረሰን።

"ጌታ ኢየሱስም "ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?" አላት።
ይህንም ብሎ በታላቅ ድምጽ "አልዓዛር ሆይ! ወደ ውጭ ና።" ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ። ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ጌታ ኢየሱስም "ፍቱትና ይሂድ ተውት።" አላቸው።"
(ዮሐ ፲፩፥፵-፵፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእናታችን ቅድስት ታኦድራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅድስት ታኦድራ <3

በዚህች ዕለት እናታችን ቅድስት ታኦድራ ትታሰባለች። ቅድስት ታኦድራ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረች ግብጻዊት ስትሆን ገዳማዊትና ሊቅ ነበረች።

ቅድስቷ ከታላላቅ የግብጽ ፓትርያርኮች (ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ፣ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ጢሞቴዎስና ቅዱስ ቴዎፍሎስ) እግር ቁጭ ብላ ተምራለች።

በተለይ በሃይማኖተ አበው የተጻፈው የቅዱስ አትናቴዎስ ድርሳን ለዚህች ቅድስት ቅዱሱ በስደት እያለ የጻፈላት እንደሆነ ይነገራል።

እርሷም ብዙ የነገረ ሃይማኖትና የሥነ ምግባር መጻሕፍትን ደርሳለች። ቅድስት ታኦድራ መልካም ገድልን ተጋድላ በመቶ ዓመቷ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዚህች ቀን ዐርፋለች።

ከቅድስቷ በረከትን አምላካችን ይክፈለን።

ሚያዝያ ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ታኦድራ ገዳማዊት
፪.አባ በኪሞስ ጻድቅ
፫.ስምኦን ዘለምጽ
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ኤጲስ ቆጶስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፬.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
፭.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።"
(፩ጴጥ ፫፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለበዓለ ዕለተ ቶማስ ወአብርሃም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

ልክ የሰሙነ ሕማማቱ ዕለታት ስምና ምሥጢር እንዳላቸው ሁሉ ከትንሣኤ በኋላ የሚገኙ ዕለታትም ስምና ምሥጢር አላቸው።

ሰኞን ቤተ ክርስቲያን "ማዕዶት" ብላ እንደምታከብር ትናንት የተመለከትን ሲሆን ማክሰኞን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን "ቶማስ" አንድም "አብርሃም" ብላ ታከብረዋለች።

<3 ቶማስ <3

ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ለጊዜው ትንሣኤ ሙታንን ከማያምኑ ሰዱቃውያን ወገን በመሆኑ የክርስቶስን ትንሣኤ ተጠራጥሮ ነበር።
ምሥጢሩ "ግን ካላየሁ ካልዳሰስኩ አላምንም።" ያለው ከፍቅሩ የተነሳ እውነት አልመስልህ ብሎት ነው።

አንድም ጌታ መለኮታዊ ጎኑን እንዲዳስሰው ቢፈቅድለት ነው። ይህች የቅዱስ ቶማስ እጅ ዛሬ ድረስ ሕያው ናት። ተአምራትንም ታደርጋለች።

<3 አብርሃም <3

ከጻድቃነ ብሊት (ብሉይ) አንዱ የሆነው አባታችን አብርሃም ከጽድቁ የተነሳ ርዕሰ አበው (የአባቶች አለቃ) ተብሏል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብርሃም ፈጣሪ ሲሆን የአብርሃም ልጅ መባልን ወዷልና።

በተለይ በከበረ ትንሣኤ የምናገኛትን መንግሥተ ሰማያት በስሙ (የአብርሃም ርስት ተብላ) ተጠርታለችና አባታችን በዚህች ቀን ይታሰባል።

እግዚአብሔር ከሁለቱ ታላላቅ ቅዱሳን ጸጋ በረከትን ያድለን።

"በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።
እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ። እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ። እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ።"
(ዕብ ፮፥፲፩-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ሰውን ስለ መውደድህ ይህን ሁሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ፡፡ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ።"
(ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ )

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለብጹዐን ጻድቃን፣ ቅዱስ ዞሲማስ እና አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ብጹዐን ጻድቃን <3

በዚህ ቀን ብሔረ ብጹዐን ውስጥ የሚኖሩ ጻድቃን ይታሠባሉ።
በሃይማኖት ትምህርት አምስት ዓለማተ መሬት አሉ። እነርሱም አቀማመጣቸው ቢለያይም ከላይ ወደ ታች፦
፩.ገነት (በምሥራቅ)
፪.ብሔረ ሕያዋን (በሰሜን)
፫.ብሔረ ብጹዐን (ብሔረ - አዛፍ - ዕረፍት) (በደቡብ)
፬.የእኛዋ ምድር (ከመሐል) እና
፭.ሲዖል (በምዕራብ) ናቸው።

ከእነዚህ ዓለማት ባንዱ የሚኖሩ የብሔረ ብጹዐን ጻድቃን፦
ኃጢአትን የማይሠሩ፣
ለአንድ ሺህ ዓመታት የሚኖሩ፣
ሐዘን የሌለባቸው፣
በዘመናቸው ሦስት ልጆችን ወልደው (ሁለት ወንድና አንድ ሴት) ሁለቱን ለጋብቻ አንዱን ለቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት የሚያውሉ ሰዎች ናቸው።

ቅዱሳኑ ወደዚህ ቦታ የገቡት በነቢዩ ኤርምያስ እና በቅዱስ እዝራ ዘመን ሲሆን አንዴ የተወሰኑት በዘመነ ሰማዕታት ወጥተው በዚህች ቀን ተሰይፈዋል።

በመጨረሻ ግን በሐሳዌ መሲሕ ዘመን ወጥተው ሰማዕትነትን ይቀበላሉ።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረቱና ይቅርታው ለምናምን ሁሉ ይደረግልን። ከደግነታቸውም በረከትን አይንሳን።

ሚያዝያ ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን የብሔረ ብጹዐን ጻድቃን
፪.ቅዱስ ዞሲማስ ገዳማዊ (ብሔረ ብጹዐንን ያየ እና ዜናቸውን የጻፈ አባት)
፫.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
፬.ቅዱስ ኤስድሮስ ሕፃን ሰማዕት (ገና በአሥር ወር ዕድሜው ሰማዕት የሆነ)
፭.አባ ሱንቱዩ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
፫.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)

"ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኑራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። እንደሚታዘዙ ልጆች ባለ ማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን 'እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።' ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።"
(፩ጴጥ ፩፥፲፫-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ ሰው ቅዱስ ኢያቄም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ኢያቄም <3

ቅዱስ ሰው ኢያቄም የሰማይና የምድር ንግሥት እመቤታችን ድንግል ማርያም አባት ነው። ቅዱሱ ከቅስራ አባቱ የተወለደ የቅዱስ ዳዊት ዘመድ ሲሆን "ኢያቄም፣ ሳዶቅ እና ዮናኪር" በሚባሉ ሦስት ሰሞቹ ይታወቃል።

ቅዱስ ኢያቄም እንደ ኦሪቱ ሥርዓት አድጎ ከነገደ ሌዊ የተወለደች የማጣትና ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ።) ሔርሜላን ልጅ ሐናን አግብቷል። ሁለቱም በንጽሕናና በምጽዋት እንደ ሕጉ ቢኖሩም መውለድ የማይችሉ መካኖች ነበሩ።

በዚህ ምክንያት ከወገኖቻቸው ሽሙጥን ታግሰው በታላቅ ሐዘን ኑረዋል። ከጊዜ በኋላ ግን ስም አጠራሯ የከበረ ደም ግባቷ ያማረ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር መረጣቸውና ከተባረከ ሰውነታቸው ድንግል ማርያምን ወለዱ።

እርሷ "ወላዲተ አምላክ" ተብላ እነርሱን "የእግዚአብሔር የሥጋ አያቶች" አሰኘቻቸው። ቅዱስ ኢያቄም እመቤታችንን ቤተ መቅደስ ካስገቡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በመልካም ሽምግልና ዐርፎ ከቅድስት ሐና ጋር በጌቴሴማኒ ተቀብሯል።

ቅዱሱ ሰው ያረፈበት ዓመት ግልጽ ባይሆንም ድንግል እመቤታችን ስምንት ዓመት ሲሞላት ሁለቱም ቅዱሳን ወላጆቿ በሕይወተ ሥጋ እንዳልነበሩ አበው ነግረውናል። በማረፍ ደግሞ ቅድስት ሐና ትቀድማለች። መቃብሩ ዛሬ ድረስ አለ። ያደለው ከቦታው ደርሶ ይሳለመዋል።

አምላካችን ከቅዱስ ኢያቄም በረከት ያሳትፈን።

ሚያዝያ ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኢያቄም (የድንግል ማርያም አባት)
፪.ቅዱስ አጋቦስ ሰማዕት
፫.ቅድስት ቴዎድራ ሰማዕት
፬.ቅዱስ አባ መቅሩፋ ጻድቅ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

"መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው።
ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል።
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው።
.....ሰው እናታችን ጽዮን ይላል።
በውስጥዋም ሰው ተወለደ።
እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።"
(መዝ ፹፮፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…
Subscribe to a channel