gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ግንቦት ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (የዓለም ሁሉ መምህር)
፪.አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ (ፍልሠታቸው)
፫.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን የተቀበለችበት)
፬.አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ
፭.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ
፮.እስክንድር ንጉሠ ኢትዮጵያ
፯.ቅዱስ መስቀል (የተአምር በዓሉ)
፰.አባታችን ያሬድ (የማቱሳላ አባት)
፱.ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፬.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
፭.ቅዱስ ድሜጥሮስ

"እናንተ የምድር ጨው ናችሁ። .....እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል። በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።"
(ማቴ ፭፥፲፫-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ
እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ
ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ
በብዙኅ ጻማ ዘአልቦ ሑጻጼ
መልዕልተ ጒንደ ዖም ነጺሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ።"

(የመላእክትን ምስጋና ለመጐብኘት ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ፈጣን ዐሳብን ወደ ልቡናው ያሳረገ ለሆነ፤ ጒድለት በሌለበት በብዙ ድካምም ወደ ዛፍ ግንድ ጫፍ ላይ ትል ሲወጣ ተመልክቶ፤ ኰብልሎ ከሄደበት መጻሕፍትን ለመማር የተመለሰ ለሆነ ለያሬድ ሰላምታ ይገባል።)
(ሊቁ አርከ ሥሉስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ <3

አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልን እንዲያው በቀድሞው አጠራር ሠለስቱ ደቂቅ (ሦስቱ ሕፃናት) እንላቸዋለን እንጂ ለእኛስ በእድሜም፣ በጸጋም፣ በትሩፋትም አባቶቻችን ናቸው።

ቅዱሳኑ የወቅቱ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጆች ናቸው። ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ሲማርክ አብረው ተማርከው ባቢሎን ወርደዋል።

ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግሥት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር። ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ። ምንም እንኳ በቤተ መንግሥት ውስጥ ቢኖሩ ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ።

አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከእነርሱ የሚደርስ አልተገኘም። ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው። ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው።

ከነገር ሁሉ በኋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ። ናቡከደነጾር ስልሳ ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ ስገዱ ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው። ነበልባሉ ከጉድጓዱ ወደ ላይ አርባ ዘጠኝ ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም።

ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልአከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው። ከሆነው ነገር የተነሳም አሕዛብ አፈሩ። ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ።

ከዚያች ቀን በኋላ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል በአት አጽንተው በጾምና በጸሎት ተወስነው ኑረዋል። ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆኗል። ቅዱስ ዳንኤልና ናቡከደነጾር ተሯሩጠው ቢሄዱ ሦስቱም በአንድነት ዐርፈው ተገኝተዋል። ንጉሡ በእጅጉ ይወዳቸው ነበርና በወርቅ በተለበጠ ሳጥን ቀብሯቸዋል። ስሞት ከመካከላቸው ቅበሩኝ በማለቱ ዛሬ ድረስ ለበቁ አባቶች የአራቱ መቃብር ባቢሎን ውስጥ ይታያል።

ቅዱሳን አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል (ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጐ) ያረፉት ግንቦት ፲ ቀን ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ አምስት መቶ ዓመት በፊት ነው።

አምላካቸው ከእሳት ባወጣቸው ቀንም፦
"ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ
ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም።" የሚለውን ምስጋና ፈጣሪ ገልጾላቸው ደርሰውታል፤ በእሳቱ ውስጥ ሆነው ተናግረውታል።

ድርሰታቸው ሁለት ወገን ሲሆን ባለ ስድስት አንቀጹ ምስጋናቸው ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚያሳይ ነው። ሌላኛውና ሠላሳ ሦስት አንቀጾች ያሉት ምስጋናቸው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለሠላሳ ሦስት ዓመታት እንደሚመላለስ ያጠይቃል።

ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በኋላ (ማለትም ከክርስቶስ ልደት በአራት መቶ ዓመታት) ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ።

ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ "አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?" አለው። ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ። በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ። ሠለስቱ ደቂቅም "ወዳጃችን! ምን ሆንክ?" አሉት።

ቅዱሱም መልሶ "ወደ ግብጽ እንሒድ። አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋችኋል።" አላቸው። እነርሱም "ለቅዱስ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው። እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ። ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም። ለክብርህ ግን እንመጣለን። ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው።" ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት። ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርም መጥቶ መልእክቱን አደረሰ። በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን ቴዎፍሎስ፣ ቄርሎስ፣ ሐጺር ዮሐንስና ሌሎችም ከምዕመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ።

እጅግ የሚደነቅ ብርሃንም ከበባቸው። በብርሃኑ መካከል ሠለስቱ ደቂቅ ሲያልፉ በጐ መዓዛ ሸተተ። ሕዝቡም በደስታና በዝማሬ የቅዱሳኑን ቅዳሴ ቤት አክብሯል።

በረከታቸው ይደርብን።

ግንቦት ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ሠለስቱ ደቂቅ ቅዱሳን (አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል)
፪.ቅዱስ አብርሃም ጸራቢ (ሰማዕት)
፫.አባ ሚካኤል ገዳማዊ
፬.አባ ይስሐቅ ግብጻዊ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
፬.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፮.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፯.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

"ናቡከደነፆርም መልሶ 'መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባርያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ።' "
(ዳን ፫፥፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራምም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ በዓለ ዕርገት እና ለጻድቁ አባ ዳንኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ዕርገተ እግዚእ <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ዕርገትን ሁለት ጊዜ ታከብራለች። አንዱ "ጥንተ በዓል" ሁለተኛው ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል። ጥንተ በዓል ማለት ጌታችን በትክክል ያረገበትን ቀን ያመለክታል።

የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በኪነ ጥበቡ (በሕማሙ በሞቱ) ዓለምን አድኖ አርባ ቀን ለሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን ትምሕርተ ኅቡዓትን አስተምሯቸዋል።

በአርባኛው ቀን መቶ ሃያውን ቤተሰብ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ወጣ። በዚያም እስከ ሊቀ ጵጵስና ድረስ ሾሟቸው። ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዝዟቸው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ጠብቁ ብሏቸዋል። እየባረካቸው በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ አርጓል።

ሰማያት፣ ምድር፣ ደመናት፣ ነፋሳት፣ መባርቅትና መላእክት ፍጥረት በሙሉ አመስግኗል። አይሁድ መናፍቃን ዕርገቱን ምትሐት ነው እንዳይሉ ጌታችን ትንሣኤውን አማናዊ እንደሆነ ለማስረዳት በአርባኛው ቀን ዐረገ።

አንድም ራስ ባለበት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊኖሩ ይገባልና ጌታችን ዕርገቱን በገሃድ አደረገው። "ዐርገ እግዚእ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን" እንዲል።
ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ።
ወእግዚእነ በቃለ ቀርን።
ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ።
(መዝ. ፵፮፥፮)

<3 ታላቁ አባ ዳንኤል <3

ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ ክቡር ነው። በሁሉ ነገሩ የተቀደሰ የገዳማውያን መብራትም ነው። ከተረፈ ንጹሕ ሕይወቱ ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን አይቷልና። አባ ዳንኤል በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ዓለምን ንቆ (መንኖ) ገዳም የገባው ገና በወጣትነቱ ነው።

ጊዜውም ዘመነ ጻድቃን (በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ነበር። በገዳመ አስቄጥስና በደብረ ሲሐት ይታወቃል። ታላቋ መካነ ቅዱሳን ገዳመ ሲሐት ዛሬም ድረስ በስሙ የምትጠራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ እጅግ ለብዙ ዘመናት በውስጧ ተጋድሎ ፍሬ ስላፈራባት ደቀ መዛሙርትን በቅድስና ስለ ወለደባት ነው።

ስለዚህም ዛሬም ድረስ "አባ ዳንኤል ዘደብረ ሲሐት" ተብሎ ሲጠራ ይኖራል። ሌላኛው ስሙ ደግሞ "ዘገዳመ አስቄጥስ" ይሰኛል። ገዳመ አስቄጥስ የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ርስት ሲሆን በዓለም በስፋትም ብዙ ቅዱሳንን በማፍራትም አንደኛ የሆነ ገዳም ነው።

በዚህ ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆኖ የሚሾሙ አበው ሁሌም የብቃት መዓርግ ላይ የደረሱ ሲሆኑ ክብራቸው ከፓትርያርክ በላይ ነው። አባ ዳንኤልም ከብዙ የቅድስና ዓመታት በኋላ በአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ እልፍ አእላፍ መነኮሳትን በጽድቅ መንገድ መርቷል።

ቅዱሱ ከትጋቱ የተነሳ ለምግብና ለእንቅልፍ ጊዜ አልነበረውም። ቀን ቀን መነኮሳቱን ሲናዝዝ፣ ድውያንን ሲፈውስ፣ ሥርዓተ ገዳምን ሲቆጣጠር ይውላል። ልክ ሲመሽ ጭው ወዳለውና ስውራን ወደ ሚገኙበት በርሃ ይወጣል።

በዚያም ሙሉውን ሌሊት የተሰወሩ አባቶችን ሲፈልግ ያድር ነበር። በዚህም ምክንያት የብዙ ስውራንን ገድል የጻፈ ሲሆን ባረፉ ጊዜም ገንዞ በመቅበር በረከታቸውን ተሳትፏል። ታላቅ ሙያንም ፈጽሟል።

እርሱ ገንዞ ቀብሮ ዜናቸውን ከጻፈላቸው ሥውራን ቅዱሳንም እንደ አብነት እስራኤላዊቷን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስን (ለሠላሳ ስምንት ዓመት ራቁቷን በሥውር የኖረች) እና ቅድስት በጥሪቃ ንግሥትን (መንግሥቷን ትታ በሥውር የኖረች ናት።) መጥቀስ እንችላለን።

ከዚህ ባለፈም አባ ዳንኤል በሰው ዘንድ የተናቁትንም ማክበርን ያውቅበታል። ለምሳሌ በሴቶች ገዳም "እብድ" ናት ተብላ በበር የተጣለችውን ቅድስት አናሲማን፣ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጳጳሳቱ ሳይቀር "እብድ" ነው ብለው የናቁትን ቅዱስ ምሕርካን እብድ ሳይሆኑ ራሳቸውን የሠወሩ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጧል።

አባ ዳንኤል ሐዋርያዊም ነበር። በጊዜው ጦማረ ልዮን የሚባል የኑፋቄ ደብዳቤ ይላክ ነበርና ለዚህ ኬልቄዶናዊ ኑፋቄ በትጋት ምላሽ ይሰጥ ነበር። አንድ ቀንም በንጉሥ ትዕዛዝ ኑፋቄው በእርሱ ገዳም ሊነበብ ሲል ቅዱሱ ከወታደሩ ቀምቶ ስለ ቀደደው ለሞት እስኪደርስ ደብድበውታል።

አባ ዳንኤል አንዴ አውሎጊስ የሚባል ድሃ ድንጋይ ጠርቦ እንግዳ ሲቀበል ተመልክቶ "ጌታ ሆይ! ይህንን ደግ ሰው ለምን ድሃ አደረከው?" ሲል በፈጣሪ ሥራ ገባ።

ጌታም እንደ ወትሮው በገሃድ ተገልጦ "በነፍስህ ትዋሰዋለህ?" አለው። "አዎ ጌታዬ" ስላለው ጌታችን ለአውሎጊስ ሃብትን ሰጠው። ግን ወዲያው የጦር አለቃና ጨካኝ ሰው ሆነ።

ጻድቁ ሰምቶ ሊጠይቅ ቢሔድ የአውሎጊስ ወታደሮች ደበደቡት። ጌታችንም አባ ዳንኤልን ወደ ፍርድ ዙፋኑ አቅርቦ "ወዳጄን መልስልኝ።" አለው። እመ ብርሃን ግን ቀርባ የልጇን እግር ሳመች።

"ልጄ ሆይ ማር!" አለችው። ጌታም "እሺ" ብሎ ጻድቁን ወደ በአቱ አውሎጊስን ወደ ቀደመ ግብሩ መለሳቸው። የአባ ዳንኤል ድንቁ ብዙ ነው።

ሌላው ቢቀር ሽፍታ አባ ዳንኤልን መስሎ ወደ ደናግል ገዳም ሊዘርፍ በማታለል ገባ። ደናግሉም ጻድቁ መስሏቸው እግሩን አጥበው ዓይነ ስውሯን ቢቀቧት ዓይኗ በርቷል። ሽፍታውም ደንግጦ ንስሐ ገብቷል። አባ ዳንኤል ግን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል።

በተረፈ ግን ከቅድስና ሕይወቱ ባሻገር፦
፩.በገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ ባሳየው ትጋት፣
፪.በሃይማኖት ጠበቃነቱ በደረሰበት ድብደባና ስደት፣
፫.ብዙ የበርሃ ቅዱሳንን በየበአታቸው እየዞረ በመቅበሩ፣
፬.የብዙ ስውራን ቅዱሳንን ዜና ሕይወት በመሰብሰቡ፣
፭.በየጊዜው በእግዚአብሔር ኃይል ይፈጽማቸው በነበሩ ተአምራትና
፮.ለድንግል እመቤታችን ማርያም በነበረው ልዩ ፍቅር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታከብረዋለች።

ቸር አምላክ ክርስቶስ ከዕርገቱና ከጻድቁ በረከት አይለየን።

ግንቦት ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን የጌታ ቤተሰብ (መቶ ሃያው)
፪.ቅዱስ አባ ዳንኤል ጻድቅ
፫.ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ መክሲሞስ መስተጋድል
፭.አቡነ ዮሐኒ ዘደብረ ዳሞ (አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ለምንኩስና ያበቁ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፫.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፬.አቡነ ኪሮስ
፭.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

"እስከ ቢታንያም አወጣቸው። እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ። ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።"
(ሉቃ ፳፬፥፶-፶፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራምም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ መቃርስ ካልዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ መቃርስ ካልዕ <3

ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ፣ መቃርስ፣ መቃሬም" ይባላል። ትርጉሙ በሦስቱም መንገድ አይለወጥም። ምክንያቱም ሥርወ ቃሉ በዮናኒ ልሳን "ብፁዕ፣ ንዑድ፣ ክቡር" ማለት ነውና።

ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ፤ ሁለተኛው" አንዳንዴ ደግሞ "እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል። "ካልዕ፤ ሁለተኛው" የሚባለው ከቀዳሚው (ታላቁ መቃርስ) ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት።

አባ መቃርስ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ገዳማዊ፣ ጻድቅና ትሩፈ ምግባር ነው። በዓለም ለአርባ ዓመት ሲኖር እንደ ሕጉ ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው። ጻድቃን እንደ ከዋክብት በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና ይህቺን ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል።

እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ ለአበው ታዝዞ በጾም፣ በጸሎት፣ በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው ፈጣሪ አከበረው። በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ ምኔት ሊሆን መረጡት።

እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን (መነኮሳትን) ከተኩላ (ሰይጣናት) ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ። ከብቃቱ የተነሳም ሳያስታጉል ሳይበላ፣ ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ አርባ ቀን ይጸልይ ነበር። ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር።

እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት እየጮሁ ይሸሹ ነበር። ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው ብዛት የተነሳ ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር። በዘመኑም ብዙ ተአምራትን ሠርቷል።

አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው። አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን ሆነው አገኛቸው። እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ ቢቀባቸው የሁሉም ዓይናቸው በርቷል።

ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ ሰጥታዋለች። (ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን አይረሱምና።) ቅዱስ መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት (አፈር) ላይ ይተኛ የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው (ቆዳው) ላይ የሚተኛ ሁኗል።

በሃገሩ እስክንድርያም ለሁለት ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት። እርሱ መጥቶ ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ። ዝናቡም ያለ ማቆም ለሁለት ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ ኃጢአታችን እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት። እርሱም በጸሎቱ (በፈጣሪው ኃይል) እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል።

የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ አልፈጽመውም። ግን አንዲት ብቻ ላክል። ሁሌ ሳስበው ስለሚገርመኝም ነው።

ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም። ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ ቦታን (አጋጣሚን) ስለምንፈልግ። በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም እንደ ተርታ ነገር (ያለ ጥንቃቄ) ስንቀበል ይታያል። ሁለቱም ግን ስሕተት ነው።

ፈርተን (ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም) ስለ ራቅን በፍርድ ቀን ማምለጥ አንችልም። "ሥጋዬን ያልበላ ደሜንም ያልጠጣ የዘላለም ሕይወት የለውም።" ይለናልና።
(ዮሐ. ፮፥፶፪)

በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል።
"ሳይገባው ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት።" ይለናልና።
(፩ቆሮ. ፲፩፥፳፯)

ታዲያ ለሁላችንም የሚሻለው ንስሐ ገብቶ በፍርሃት ሆኖ መቅረቡ ነው።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር። ቅዱሱ ይህንን እያሰበ ለስልሳ ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል። ለዚያ አይደል አበው "ብታከብሩት ያከብራችኋል" ያሉት።
ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ፦
"ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ።
አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ።
መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ።
ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ።
መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ።" ብለዋል።

ቅዱስ መቃርስም በመቶ ዓመቱ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል።

ጌታችን ከክብሩ ከበረከቱ አይለየን።

ግንቦት ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳማዊ
፪.እናታችን ቅድስት ሰሎሜ ኢትዮጵያዊት
፫.አባ ይስሐቅ ጻድቅ
፬.ቅድስት ዲላጊና አራት ሴት ልጆቿ (ሰማዕታት)
፭.ቅዱስ ዳናስዮስ ሰማዕት
፮.ቅዱስ በንደላዖስ ሰማዕት (የታላቁ ኤስድሮስ አባት)
፯.አባ አሞን ጻድቅ (ጵጵስናን አልፈልግም ብሎ የሸሸ አባት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል። እኔም በእርሱ እኖራለሁ።"
(ዮሐ ፮፥፶፬-፶፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ መልከ ጼዴቅ <3

ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መልከ ጼዴቅን ብዙ ሰው ሽዋ (ሚዳ) ውስጥ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማቸው ያውቃቸዋል። ገዳሙ በእድሜ ጠገብ ዛፎች ያጌጠ ከመሆኑ ባሻገር በጻድቁ ቃል ኪዳን ምክንያት በቦታው የሚቀበር ሁሉ አካሉ አይፈርስም።

የጻድቁስ ዜና ሕይወታቸው እንደምን ነው ቢሉ፦
አቡነ መልከ ጼዴቅ በሸዋ ነገሥታት ዘመን የነበሩ የንጉሡ ዓምደ ጽዮን የቅርብ ዘመድ ነበሩ። የጻድቁ ወላጆች ፍሬ ጽዮንና ዓመተ ማርያም ይባላሉ። አቡነ መልከ ጼዴቅ ገና በሕፃንነታቸው ሥርዓተ መንግሥትን አጥንተዋል።

በኋላ ከመምህር ዘንድ ገብተው ብሉይ ከሐዲስ ተምረው ሲያጠናቅቁ ይህንን ዓለም ናቁና ከቤተ መንግሥቱ አካባቢ ጠፍተው ወደ አቡነ አሮን መንክራዊ ዘንድ ሔደው መንኩሰዋል።

ነገሩ በቤተ መንግሥት አካባቢ ሲሰማ ወላጆች አለቀሱ። አቡነ አሮንም ተከሰው ነበር። ነገሩ ግን ከእግዚአብሔር ነበርና አቡነ መልከ ጼዴቅን መልአክ እየመራ አምጥቶ አሁን ገዳማቸው ያለበት ሸዋ (ሚዳ) አደረሳቸው።

በዚያ ትንሽ በዓት ሰርተው ለዘመናት ተጋድለዋል። ዋሻዋም ደብረ መድኃኒት ትባላለች። ጻድቁ ከጾምና ጸሎታቸው በተረፈ ዓርብ ዓርብ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት በማሰብ ጀርባቸውን ሦስት መቶ ጊዜ ይገርፉ ደቀ መዛሙርቱንም ግረፉኝ ይሉ ነበር። አንድ ጊዜም እጃቸውንና እግራቸውን በትልልቅ ችንካሮች ቸንክረውት ደማቸው ሲፈስ ተገኝቷል።

በመጨረሻ አቡነ መልከ ጼዴቅ ጌታን "ኢትዮጵያውያንን ማርልኝ?" አሉት። ጌታችንም መለሰ "በስምህ ያመኑትን በቃል ኪዳንህ የተማጸኑትን ገዳምህን የተሳለሙትን እምርልሃለሁ።"

ጻድቁም ብዙ ተአምራትን ሰርተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። አቡነ አምሃ ኢየሱስም በክብር ገንዘው በበዓታቸው ውስጥ ቀብረዋቸዋል።

አምላካችን እግዚአብሔር ከጻድቁ ዋጋና በረከት አይለየን።

ግንቦት ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ መልከ ጼዴቅ ካህን (ኢትዮጵያዊ ጻድቅ)
፪.አባ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት
፫.ቅዱሳን ሶሲማና ኖዳ ሰማዕታት (የታላቁ ፊቅጦር ተከታዮች የነበሩ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ (ወንጌላዊው)
፪.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

"ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትን ወደ እርሱ ይጥራ። በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፤ ጌታም ያስነሳዋል። ኃጢአትም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሠረይለታል። እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።"
(ያዕ ፭፥፲፬-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ የትዕግስት ሰው ቅዱስ ኢዮብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ኢዮብ <3

የትዕግስት አባት ቅዱስ ኢዮብ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ እንደተመለከትነው ያልተፈተነበት ነገር የለም። ሐረገ ትውልዱም ከአባታችን አብርሃም ይመዘዛል።
አብርሃም ይስሐቅን
ይስሐቅ ኤሳውን
ኤሳው ራጉኤልን
ራጉኤል ዛራን
ዛራ ኢዮብን ይወልዳሉ።

ቅዱስ ኢዮብ የነበረው እስራኤል በግብጽ በባርነት ሳሉ ነበር። ኢዮብ ይህ ቀረህ የማይሉት ባለጠጋ፣ ደግና እግዚአብሔርን አምላኪ ነበር። የኢዮብ ደግነት የተመሰከረው በሰው (በፍጡር) አንደበት አልነበረም። በራሱ በፈጣሪ አንደበት እንጂ።

በዚህ የቀና ጠላት ዲያብሎስ ግን ኢዮብን ይፈትነው ዘንድ ከአምላክ አስፈቀደ። ጌታችን የጻድቁን የትዕግስት መጠን ሊገልጥ ወዷልና ሰይጣን ኢዮብን በሃብቱ መጣበት። በአንድ ጀምበርም ድሃ ሆነ። እርሱ ግን ፈጣሪውን ባረከ።

ሰይጣን ቀጠለ የአብራኩን ክፋዮች (ልጆቹን) አሳጣው። ኢዮብ አሁንም አመሰገነ።

በሦስተኛው ግን ሰውነቱን በቁስል መታው። ቁስል ሲባል በዘመኑ እንደምታዩት ዓይነት አልነበረም። ከሰው ሕሊና በላይ የሆነ አሰጨናቂ ደዌ ነበር እንጂ። ጻድቁ የአንድ ወጣት እድሜ ያሕል በመከራው ጽናት እየተሰቃየ ገላውን በገል ያከው ነበር። ከአፉ ግን "ተመስገን!" ማለትን አላቋረጠም።

በመጨረሻም ሰይጣን በሚስቱ መጣበት። "እግዚአብሔርን ተሳደብ።" አለችው። እርሱ ግን መለሰ "እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ነሣ። ስሙ የተባረከ ይሁን።"

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ እግዚአብሔር ሰይጣንን ከጎዳናው አስወገደው። ጤናውን፣ ሃብቱን፣ ልጆቹን ለኢዮብ መለሰለት። ካለው እድሜ ላይ መቶ ሰባ ዓመት ጨመረለት። ጻድቅና የትዕግስት ሰው ቅዱስ ኢዮብ በሁለት መቶ አርባ ስምንት ዓመቱ በዚህች ቀን ዐረፈ።

እግዚአብሔር አምላክ ከጻድቁ ትዕግስትና በረከት አይለየን።

ግንቦት ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ
፪.አባ ቴዎድሮስ ሊቀ ምኔት (የታላቁ ቅዱስ ጳኩሚስ ደቀ መዝሙርና የአቡነ አረጋዊ ጓደኛ)
፫.ሃያ ሁለት ሰማዕታት (የአባ ኤሲ ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
፭.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፮.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

"ወንድሞች ሆይ! የመከራና የትዕግስት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። እነሆ በትዕግስት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን። ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል። ጌታም እንደፈጸመለት አይታችኋል። ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።"
(ያዕ ፭፥፲-፲፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ተፈሥሐት ምድር ወሰማይ አንፈርዐጸ
በዕለተ ጸገዩኪ አብላስ ወአውጽኡ ሠርጸ
ተአምረ ሕይወት ማርያም ዘአልብኪ ቢጸ
እስከ ፈርሀ መልአከ ሞት ወሰይጣን ደንገጸ
ዜና ልደትኪ ነጐድጓድ እስከ (ውስተ) ሲኦል ደምፀ።"
(በለሶች (ኢያቄምና ሐና) ቡቃያ አንቺን ባስገኙሽ ጊዜ ምድር ደስ አላት፤ ሰማይም ደስ አለው። ጓደኛ (ምሳሌ) የሌለሽ የድኅነት ምልክት ማርያም፤ መልአከ ሞት እስከ ፈራና ሰይጣንም እስከ ደነገጠ ድረስ የመወለድሽ ዜና እስከ ሲኦል ድረስ (በሲኦል) ተሰማ።)
(አባ ጽጌ ድንግል ወአባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ልደታ ለማርያም ድንግል <3

"ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ።
ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ።
ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን።
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን። (ወለደች - አስገኘችልን።)"

የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል፤ ተመስግነዋል። ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኳ መሆን የማይችል የሰማይና የምድር ንግሥት የእግዚአብሔርን እናት እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን።

ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ። እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ጸልየዋል። ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል።
ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች።
(ኢሳ. ፩፥፱)

ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህች ቀን በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች።
"ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ።"
(መኃ. ፬፥፰)

ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች ልጅ የላችሁም በሚል ይናቁ ነበር።

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት - ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ።
እነርሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም።

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው። አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች። "እንስሳትና አራዊትን እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች።

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ። ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ። በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ። እርሱ ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ በማኅጸኗ ስትደርስ አየ።

እርሷ ደግሞ የኢያቄም በትር አብቦ አፍርቶ ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች። ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን።" አሉ። ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ።

በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ ሰባት) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ። "ዓለም የሚድንባት የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ።" ብሏቸው ተሠወረ። እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች።
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ.....
ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም።" እንዳለ ሊቁ።
(ቅዳሴ ማርያም)

"ለጽንሰትኪ በከርሥ እንበለ አበሳ ወርኩስ ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ....."
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው፤ የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው።"
(መጽሐፈ ሰዓታት፣ ኢሳ. ፩፥፱)

እመቤታችን ነሐሴ ሰባት ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች።
የእመቤታችን የዘር ሐረግ፦
አዳም - ኖኅ - አብርሃም - ይስሐቅ - ያዕቆብ
በእናቷ፦ ሌዊ - ቀዓት - እንበረም - አሮን - ቴክታና በጥሪቃ - ሔኤሜን - ዴርዴን - ቶና - ሲካር - ሔርሜላና ማጣት - ሐና።
በአባቷ በኩል፦ ይሁዳ - ፋሬስ - ሰልሞን - ቦኤዝ - እሴይ - ዳዊት - ሰሎሞን - ሕዝቅያስ - ዘሩባቤል - አልዓዛር - ቅስራ - ኢያቄም ይሆናል።

<3 ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ ወላዲተ አምላክ ተወለደች። <3

የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ፣ ፍቅሯ፣ ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን።

ግንቦት ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ልደታ)
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቴክታና በጥሪቃ
፬.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ (የእመቤታችንን ቅዳሴ የደረሰበት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

"መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው።
ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል።
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው።.....
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል።
በውስጧም ሰው ተወለደ።
እርሱም ራሱ ልዑል መሠረታት።"
(መዝ ፹፮፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ ወሰማዕት አባ ሜልዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሜልዮስ ሰማዕት <3

ቅዱስ ሜልዮስ ልጅነቱን በመንፈሳዊ ትምህርት ያሳለፈ በጉብዝናው ወራት ፈጣሪውን ያሰበ ደግ ክርስቲያን ነው። ይህችን ዓለም ከነ ክፋቷ ንቆ ኮራሳት ወደሚባል በርሃ ሔዶ በተራራውና በደኑ ውስጥ በጾምና በጸሎት በትሕርምትም ለበርካታ ዓመታት ተጋድሏል።

በእነዚህ የብሕትውና ዘመናቱ ልብሱን ፀሐይና ብርድ ቆራርጦ ስለ ጨረሳቸው ፈጣሪው ጸጉርን አልብሶታል። የአባ ሜልዮስ ጸጉሩ እስከ እግሩ ጽሕሙ እስከ ጉልበቱ ነበር።

እድሜው ገፍቶ ሲያረጅ እንዲያገለግሉት እግዚአብሔር ሁለት ወጣት ምስጉን ክርስቲያኖችን ላከለት። እነርሱም አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ ይባላሉ። ሁለቱ ቅዱሳን አምላካቸውን እግዚአብሔርንና አባታቸው ቅዱስ ሜልዮስን በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል።

ከቆይታ በኋላ ግን በአካባቢው የነበሩ ጣዖት አምላኪዎች አራዊት እናጠምዳለን ብለው በዘረጉት መረብ ቅዱስ ሜልዮስን ያዙት። ክርስቲያን መሆኑን ሲያውቁ "ለፀሐይ ስገድ።" ብለው ደበደቡት።

ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው መጥተው አባታቸውን በመከራ መሰሉት። ክርስቶስን አንክድም ስላሉ ሁለቱንም በሰይፍ አንገታቸውን መቷቸው። ቅዱስ ሜልዮስን ግን ለአሥራ አምስት ቀናት ካሰቃዩት በኋላ በዚህች ቀን በቀስት በተደጋጋሚ ወግተው ገድለውታል። ጻድቅና ሰማዕት ቅዱስ ሜልዮስ ብዙ ተአምራትን አድርጓል።

ገዳዮች ግን ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ የሜዳ አህያ ሊያድኑ የወረወሩትን ቀስት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እነርሱ መልሶባቸው ልብ ልባቸውን ተወግተው ሙተዋል።

ቸሩ አምላካችን ከቅዱስ ሜልዮስና ከደቀ መዛሙርቱ በረከትን ያካፍለን።

ሚያዝያ ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሜልዮስ ዘደብረ ኮራሳን (ጻድቅና ሰማዕት)
፪.አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ (ደቀ መዛሙርቱ)
፫.ቅዱስ ብስጣውሮስ ሰማዕት (ተንባላት የገደሉት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

"ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው። አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን። የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።"
(ራእይ ፪፥፲)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"እኔ የማምነው በአንድ እግዚአብሔር ነው። የምቀበለው የነጻነታችን ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነው። ኢጣሊያ የሚባል ገዥ አላውቅም። ለፋሺስት ኢጣሊያ የተገዛ እንደ አርዮስ የተረገመ ይሁን። እንኳንስ ሕዝቡ ምድሪቱም እንዳትገዛላቸው አውግዣለሁ።"
(ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቀዳማይ ዘጎሬ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ማር ፊቅጦር <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደማቸውና በገድላቸው ያስጌጡ ብዙ ሰማዕታት አሉ። ነገር ግን ከኮከብም ኮከብ ይበልጣልና ማን እንደ ጊዮርጊስና እስጢፋኖስ!

ከእነርሱ ቀጥለው ከሚጠሩ ሰማዕታት ደግሞ አንዱና ዋነኛው ቤተ ክርስቲያን "ማር" የምትለው ቅዱስ ፊቅጦር ነው።
እስኪ ከበዛው መዓዛ ገድሉ ጥቂት እንካፈል።

ቅዱስ ፊቅጦር አባቱ ኅርማኖስ ይባላል። አረማዊና ጨካኝ ነው። እናቱ ግን የተመሰገች ቅድስት ማርታ ትባላለች። ልጇን እንደሚገባ አሳድጋው ሃያ ዓመት ሲሞላው የአንጾኪያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃና በመንግሥቱ ሦስተኛ አድርጐ ሾመው።

የድሮዋ አንጾኪያ (ሮም) ዓለምን የተቆጣጠረች ሃገር ነበረች። ቅዱስ ፊቅጦር ደም ግባቱ ያማረ በጦርነትም ኃይለኛ ስለ ነበር ሁሉ ያከብሩት ይወዱትም ነበር። እርሱ ግን ቀን ቀን ሲጾም ነዳያንን ሲያበላ ይውል ነበር።

ሌሊት ደግሞ እኩሉን ሲጸልይና ሲሰግድ እኩሉን የእስረኞችን እግር ሲያጥብ ያድር ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆንኮ እርሱ የንጉሡ ሦስተኛ የሠራዊትም አለቃ ነው። በዘመኑ የሚያገድፍ ምግብና የወይን ጠጅ በአፉ ዙሮ አያውቅም።

ከነገር ሁሉ በኋላ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ካደ። ዘመነ ሰማዕታትም ጀመረ። አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ። ከአርባ ሰባት ሚሊየን በላይ ክርስቲያኖች በመንኮራኩር ተፈጩ፣ በመጋዝ ተተረተሩ፣ ለአራዊት ተሰጡ፣ በግፍም ተጨፈጨፉ። ቀባሪ አጥተውም ወደቁ።

በዚህ ጊዜ ማር ፊቅጦር እናቱን ቅድስት ማርታን በዕንባ ተሰናብቶ ወደ ንጉሡ ቀርቦ በክርስቶስ ስም ታመነ። ክፉ አባትም በልጁ ላይ ሞትን መከረ።

ከዚያም ቅዱሱን አፉን በብረት ለጉመው ወደ ምድረ ግብጽ አወረዱት። መሪያቸው እንዳልነበረ ወታደሮቹ መኳንንቱ ሁሉ ተዘባበቱበት። እርሱ ከምድራዊ ንግሥና ሰማያዊ መንግሥትን በሰዎች ፊት ከመክበር ስለ ክርስቶስ ሲል መናቅን መርጧልና።

ለቀናት፣ ለወራትና ለዓመታት መኳንንቱ እየተፈራረቁ አሰቃዩት። በእርሱ ላይ ያልሞከሩት የስቃይ ዓይነት አልነበረም። አካሉን ቆራርጠዋል፣ ዓይኖቹን አውጥተዋል፣ ምላሱንም ቆርጠዋል።

በዚህች ዕለት ግን በሰይፍ አንገቱን ቆርጠውታል። ስለዚህም እናት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ማክበር ታከብረዋለች። እግዚአብሔርም ለቅዱስ ፊቅጦር እንዲህ አለው፦ "እንደ አቅሙ ስምህን የጠራ፣ መታሠቢያህን ያደረገ፣ ስምህን ያከበረ የብርሃን ልብስ አጐናጽፌ ወደ መንግሥተ ሰማያት አስገባዋለሁ።"

ቸሩ አምላከ ፊቅጦር ሁላችንም ይማረን። ከቃል ኪዳኑ አሳትፎ ለርስቱ ያብቃን።

ሚያዝያ ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ጽኑዕና ኃያል ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
፪.ቅድስት ማርታ (የፊቅጦር እናት)
፫.ብጽዕት እስጢፋና (በክርስቶስ ስላመነች ከሁለት ሰንጥቀው የገደሏት የአሥራ አምስት ዓመት ወጣት)
፬.ቅዱሳን ሳሲማና አባ ኖባ (ሰማዕታት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪.አቡነ መብዐ ጽዮን ጻድቅ
፫.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፮.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

"እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና። በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።"
(ዕብ ፮፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእናታችን ቅድስት ሣራ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅድስት ሣራ <3

እናታችን ቅድስት ሣራ በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩ ክርስቲያኖች አንዷ ናት። ተወልዳ ያደገችው በሃገረ አንጾኪያ (ሶርያ) ውስጥ ነው። ለክርስቲያን እንደሚገባ አድጋ በመንፈሳዊ ሥርዓት አግብታለች።

የመከራው ዘመን እየገፋ ሲመጣ ባሏ ሃይማኖቱን በመካዱ ሕይወቷ ተመሰቃቀለ። በመሐል ላይ ደግሞ ነፍሰ ጡር ነበረችና መንታ ልጆችን ወለደች። ልጆቿን ክርስትና ለማስነሳት ምድረ ሶርያን ዞረች፤ ግን አልቻለችም።

ምክንያቱም ከመከራ ብዛት አብያተ ክርስቲያናት የሚበዙቱ ተቃጥለውና ፈርሰው ነበር። ቀሪዎቹ ደግሞ ካህናትና ምዕመናን በማለቃቸው ምክንያት ተዘግተው ነበር።

ቅድስት ሣራ ልጆቿ የሥላሴ ልጅነትን ሳያገኙ እንቅልፍ ሊወስዳት አልቻለምና ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል ግን መንፈሳዊ ውሳኔን ወሰነች። ከሶርያ ተነስታ በመርከብ ተጭና ወደ ግብጽ ወረደች።

በውኃው መካከል ላይ ሲደርሱ ታላቅ ማዕበል ተነስቶ አናወጣቸው። በዚህ ጊዜ ቅድስት ሣራ ደነገጠች። ልጆቿ ጥምቀትን ሳያገኙ መሞታቸው ነውና በእምነት ወደ ፈጣሪዋ ጸለየች። ሁለቱን ልጆቿን ወስዳ በባሕሩ ላይ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቃ ከጡቷ አካባቢ በጥታ በሜሮን አምሳል ቀባቻቸው።

ድንገት ግን በዚህ አፍታ ማዕበሉ ጸጥ አለ። እርሷም እያደነቀች ወደ ግብጽ ደርሳ ሊቀ ጳጳሳቱን (ቅዱስ ጴጥሮስን) "አጥምቅልኝ" አለችው። ቅዱስ ጴጥሮስም ሥርዓቱን አድርሶ ሊያጠምቃቸው ባልዲውን ሲዘቀዝቀው ውኃው ረጋበት። ሁለተኛም ሦስተኛም ሞከረ። ግን አሁንም ለሌሎቹ ሕፃናት የሚፈሰው ለቅድስት ሣራ ልጆች እንቢ አለ።

ቅድስት ሣራም "ምናልባት በድፍረቴ ምክንያት ይሆናል።" ብላ የሆነውን ሁሉ እያዘነች ነገረችው። ቅዱስ ጴጥሮስ ግን እግዚአብሔርን አመሰገነ። አላትም "ፈጣሪ ባንቺ እጅ ስላጠመቃቸው የእኔን እንቢ አለ። ልጄ ሆይ! ሃይማኖትሽ ትልቅ ነው።"

ከዚህ በኋላም ሥጋውን ደሙን አቀብሎ ባርኮ አሰናብቷታል። ወደ ሶርያ ስትመለስ ግን ሌላ የከፋ ነገር ጠበቃት። በባሏ ከሳሽነት ወደ ከሃዲው ንጉሥ (ዲዮቅልጥያኖስ) ቀረበች። ንጉሡ ክርስቶስን ካጂ የት እንደ ነበርሺም ተናገሪ አላት። እርሷ ግን ሃይማኖቷ የጸና ነበርና እንቢ አለች።

በዚህም ምክንያት በ፫፻ ዓ.ም አካባቢ በዚህች ቀን አንድ ልጇን በሆዷ ሌላኛውን በጀርባዋ አድርገው በእሳት አቃጥለው ገድለዋታል። እነሆ ቤተ ክርስቲያን ታስባታለች፤ ታከብራታለችም።

አምላካችን ቅድስት ሣራን እንዳጸና እኛንም ያጽናን። ከበረከቷም ያድለን።

ሚያዝያ ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ሣራና ሁለቱ ልጆቿ (ሰማዕታት)
፪.አቡነ ገብረ ማርያም ጻድቅ - ዘልሆኝ (ኢትዮጵያዊ)
፫.አባ በብኑዳ ባሕታዊ
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ መስተጋድል
፭.ቅድስት ዶራ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፮.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን? 'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን።' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ ፰፥፴፭-፴፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ።"
(ቅዱስ ኤፍሬም)

እንኳን ለታላቁ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ዐቢይ ወክቡር ጊዮርጊስ ሰርዌ አዕላፍ ወመክብበ ሰማዕታት <3

መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰባት ዓመታት ስቃይ በኋላ በዚህች ቀን ተሰይፏል።
ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ፦
ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃያ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሥልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ (ደራጎን) ሲያመልኩ አገኛቸው። እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ፣ አሳምኖ፣ ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ሰባ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር። በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው። እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ።

ከዚያም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ። ሦስት ጊዜ ሙቶ ተነሳ። ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው፣ ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል።
"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ።" እንዲል መጽሐፍ።

ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው። ሰባ ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ።

በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ። ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት። ያለ ርኅራኄም አካሉን አሳረሩት። ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት።

በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት።
"ሐረድዎ ወገመድዎ ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል።
(ምቅናይ)

እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች፣ ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ።

ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ።" ብሎ አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው። ሰባው ነገሥታት ግን አፈሩ።

ከሰባት ዓመታት መከራ በኋላም በዚህች ቀን ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም፣ ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል። ሰባት አክሊላትም ወርደውለታል።
በ፫፻፺ዎቹ አካባቢ ሰማዕት ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በዚያው በሃገሩ ደብር አንጸው አጽሙን አፍልሠው ቀድሰዋታል።

ቅዱሱ ሰማዕት ከሰማዕትነቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተአምረኛ ነው። በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ከነበሩ አራዊት (ነገሥታት) መካከል አንዱ የሆነው ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም የአርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን ደም አፍስሶ ነበርና ፈጣሪ ደመ ሰማዕታትን የሚበቀልበት ጊዜ ደረሰ።

በ፫፻፭ ዓ.ም አካባቢ አረመኔው ንጉሥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተአምረኛነት ሰምቶ እንዲያፈርሱት ሠራዊት ላከ። የሠራዊቱ አለቃም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ላይ ተሳለቀ።

ከፊቱ የነበረውን ቀንዲል በሰይፍ እመታለሁ ሲል ግን ቀንዲሉ ተገልብጦ መሐል አናቱን መታው። እንደ እብድ ሆኖ ሞተ። ሠራዊቱም ሰምቶ ወደ ንጉሡ ሸሸ። ይህን ሰምቶ የተበሳጨው ዲዮቅልጢያኖስ ግን ራሱ ሊያፈርሰው ሔደ። ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ሲደርስ ሚካኤልና ገብርኤል ዓይኑን አጠፉት።

እገባለሁ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ መረዋውን (ደወሉን) ለቀቀበት። ራሱን ቢመታው ደነዘዘ። የብዙ ቅዱሳንን ደም የጠጣው ርጉሙ ንጉሥም አብዶ ለሰባት ዓመታት ፍርፋሪ ሲለምን ኑሮ ሰይጣን ከገደል ጫፍ ወርውሮ ገድሎታል።

አምላካችን እግዚአብሔር ከኃያሉ ሰማዕት ጽናትና ትዕግስት፣ በረከትም ይክፈለን።

ሚያዝያ ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፪.ቅዱስ ሮቆ ጻድቅ (በስሙ ለተማጸነ ከወባ በሽታ እንዲጠብቀው ጌታ ቃል ኪዳን የገባለት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
፫.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፬.አባ ሳሙኤል
፭.አባ ስምዖን
፮.አባ ገብርኤል

"የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ። ተፈተኑ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዓለም ሁሉ መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እና ለኢትዮጵያውያኑ ቅዱሳን ተክለ ሃይማኖት ወክርስቶስ ሠምራ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ <3

ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ፣ ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሐ ስለእርሱ ሊናገር አይቻለውምና። አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር "አፈ ወርቅ" መሆን ያስፈልጋል። እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ነገዱ ከሶርያ የተወለደው በ፫፻፵፯ ዓ.ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ። እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው። ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምህርትና በጥበብ አደገ። ገና በሕፃንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው። በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በአሥራ አምስት ዓመቱ ነበር። በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው።

ቅዱሱ ገና በአሥራ ስድስት ዓመቱ ሃብት፣ ንብረት፣ ውበት፣ ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ። ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ እርሱ መጡ። ሊቀ ሐዋርያት የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ ሥልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት።

ከዚህች ዕለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምሥጢራት ሆነ። ብሉይ ከሐዲስ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራእየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጓሜ ተነተናቸው። በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው። ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት፣ መልዕክታትና ትርጓሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ። በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ ማዕርጉም ዲቁና ነበር።

ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ። በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት። አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም። ከጣዕመ ትምህርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር። ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር። አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል "አፈ ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች። ለዚያም ነው "አፈ ወርቅ" የሚባለው። ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልአከ ሞትን ገስፆ አሥር ዓመት አቁሞታል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም። በእርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው። ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር። ምክንያቱም የወቅቱ ንግሥት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ "አልመልስም" በማለቷ መክሮ አወገዛት። እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ ሁለት ጊዜ አጋዘችው። በተሰደደበት ሃገር ፍሬ አፍርቶ፣ አስተምሮና አሳምኖ በ፬፻፯ ዓ.ም ዐርፏል። ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በስልሳ ዓመቱ አጡት። በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ።

ከዕረፍቱ አስቀድሞ አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ። (ግብዣ አዘጋጀ።) በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) ከሰማይ በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ።

ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ?" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን። እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና።" አሉት። "እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንዲገለጥልኝ መርቁኝ።" አላቸው። ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ።

በማግስቱ በቤተ መንግሥት ውስጥ ሊቃውንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ጳጳሳቱ፣ ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም። ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ?" ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው።

"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ - የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም።' ማለቱ (ማቴ. ፩፥፳፭) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር።

"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች። ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል። እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር።
'እርሷ ማን ናት? በማኅጸኗ ያለውስ ማን ነው?' እያለ ይጨነቅ ነበር። ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና። አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም።አሁን ግን ልጇ አምላክ ዘበአማን እርሷም ወላዲተ አምላክ መሆኗን አወቀ ማለት ነው።" እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ በዚያ የነበረች ሥዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች።

ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በሥዕሏ ላይ አደረገ። አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ ....." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት። ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል።

ቅዱሱ ሲጠራ እንዲህ ነው፦
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
አፈ በረከት
አፈ መዐር (ማር)
አፈ ሶከር (ስኳር)
አፈ አፈው (ሽቱ)
ልሳነ ወርቅ
የዓለም ሁሉ መምህር
ርዕሰ ሊቃውንት
ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
ሐዲስ ዳንኤል
ሊቀ ጳጳሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
መምህር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
ጥዑመ ቃል .....

እግዚአብሔር ከቅዱሱ በረከት አብዝቶ፣ አብዝቶ፣ አብዝቶ ይክፈለን።

ዳግመኛ በዚህች ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥጋቸው ፈልሷል። ይህ የተደረገው ጻድቁ ካረፉ ከሃምሳ ስድስት ዓመታት በኋላ ነው። በዕለቱም ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተፈጽመዋል።

እናታችን ርኅርኅቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደግሞ በዚህች ቀን ስሟን ለጠራና መታሠቢያዋን ላደረገ የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች።

ቸር አምላካቸው ከሁለቱም ብሩሃን ቅዱሳኑ ክብር ያድለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ <3

ቅዱስ ያሬድ ከእግዚአብሔር ያገኘነው አባታችን፣ ክብራችን፣ ሞገሳችን ነውና በምን እንመስለዋለን?
አንደበቱ ጣፋጭ (ጥዑም)፣
ልቡናው የቅድስና ማኅደር፣
ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ ነው።
እስከ አርያም ተነጥቆ የማይፈጸም ምሥጢርን የተመገበ ማን እንደ እርሱ!

ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት "ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ሙሉ አካሏ ነው።"

ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ፭፻፭ ዓ.ም አክሱም አካባቢ ሲሆን እናቱ ክርስቲና (ታኡክልያ) አባቱ ደግሞ ይስሐቅ (አብድዩ) ይባላሉ። ሊቁ በሕፃንነቱ ምሥጢር (ትምህርት) አልገባው ብሎ ይቸገር ነበር። ትምህርት እንቢ ያለው ሰነፍ ስለ ነበር አይደለም። በጥበበ እግዚአብሔር እንጂ።

ምንም ትምህርት ባይገባው ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር። ልቡናው ደግሞ በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር የታሠረ ነበር። አንድ ቀን ግን መምህሩ የነገሩት ቀለም አልያዝህ አለው። ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ።

ዱላው በጣም ስለ ተሰማው ቅዱሱ ከመምህሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው። ትሏ ስድስት ጊዜ ወድቃ በሰባተኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቅርታ ጠይቆ ትምህርት ጀመረ። ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ። እግዚአብሔር ደግሞ በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው።

ካህኑ ያሬድ እንዲያ አልገባህ ያለው ምሥጢር ተገልጦለት በጥቂት ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ወሰነ። በምሥጢር ባሕርም ይዋኝ ጀመር።

ያን ጊዜ ሰማያዊ ዜማ አልተገለጠም ነበርና በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት። ሦስት መላእክት በሦስት ወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት። ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት። ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር፣ ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ። ይህንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት።

ሊቁ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ተመስጦ አክሱም ጽዮን ውስጥ በሃሌታ አመሰገነ። ሕዝቡና ንጉሡም ከጣዕሙ የተነሳ አደነቁ። ቅዱስ ያሬድ ለተወሰነ ጊዜ በአክሱምና ደብረ ዳሞ ሲያገለግል ቆይቶ ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ብሎ ለእመቤታችን አንቀጸ ብርሃንን ደርሶላት ከሃገሩ ወጣ።

ቅዱስ ያሬድ በቀሪ የሕይወቱ ዘመናት
፩. አምስት ያሕል መጻሕፍትን ጽፏል።
፪. በጣና ቂርቆስ፣ በዙር አባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል።
፫.በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሃ መላእክትና በተባሕትዎ ኑሯል።

በ፭፻፸፮ (፭፻፸፩) ዓ.ም በተወለደ በሰባ አንድ ዓመቱ በዚህች ቀን ተሰውሯል።

አባቶቻችን፦
ጥዑመ ልሳን
ንሕብ
ሊቀ ሊቃውንት
የሱራፌል አምሳያ
የቤተ ክርስቲያን እንዚራ
ካህነ ስብሐት
መዘምር ዘበድርሳን
ማኅሌታይ
ልዑለ ስብከት እያሉ ይጠሩታል።

የቅዱሱ ጸሎትና በረከት ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን።

ግንቦት ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን ወማኅሌታይ
፪.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
፫.ቅዱሳን ክርስቲናና ይስሐቅ (የቅዱስ ያሬድ ወላጆች)
፬.ቅድስት ታውክልያ እናታችን (ንግሥናን ንቃ ሰማዕት የሆነች)
፭.ቅድስት ኤፎምያ ሰማዕት
፮.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፯.ቅድስት አናሲማ ገዳማዊት
፰.አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ
፱.አባ አሴር ሰማዕት (ኢትዮጵያዊ)
፲.አባ በኪሞስ ጻድቅ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
፪.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፫.ብፁዐን ኢያቄምና ሐና

"እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ። በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም። እግዚአብሔር ያውቃል። ወደ ገነት ተነጠቀ። ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።"
(፪ቆሮ ፲፪፥፪-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራምም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእናታችን ቅድስት እሌኒ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 እሌኒ ንግሥት <3

ቅድስት እሌኒ የታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱና እግዚአብሔር ለበጐ አገልግሎት የጠራት ቡርክት ሴት (ንግሥት) ናት።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
የቅድስቲቱ ሃገረ ሙላዷ ሮሃ (ሶርያ) አካባቢ ነው። ነገዷ ከእስራኤል ዝርዋን እንደሆነም ይነገራል። ጣልያኖች "Helena" በእንግሊዝኛው "Helen" ይሏታል። እኛ ደግሞ "እሌኒ" እንላታለን። ትርጓሜው "ጥሩ ምንጭ" አንድም "ውብና ደግ ሴት" ማለት ነው።

ቅድስት እሌኒ በመልካም ክርስትና አድጋ እንደ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተርቢኖስ የሚባል ነጋዴ አግብታ ነበር። ወቅቱም ዘመነ ሰማዕታት ነበር። በማይሆን ነገር ጠርጥሮ ባሕር ላይ ጥሏት ንጉሥ ቁንስጣ አግኝቷታል። እርሱም የበራንጥያ (የኋላዋ ቁስጥንጥንያ) ንጉሥ ነበር።

ቅድስት እሌኒ ከቁንስጣ የተባረከ ልጅን ወለደች። ቆስጠንጢኖስ አለችው። በልቡናው ፍቅርን፣ ርኅራኄን፣ መልካምነትን እየዘራች አሳደገችው። ቅዱሱ አባቱ በሞተ ጊዜ ተተክቶ ነገሠ።

ቅድስት እሌኒንም ንግሥት አደረጋት። ያንን የአርባ ዓመት ግፍ በአዋጅ አስቀርቶ ለክርስቲያኖች ነፃነትን ክብርን በይፋ ሰጠ። አንድ ሁለት ብለን የማንቆጥረውን ውለታ ለምዕመናን ዋለ። ከእነዚህ መልካም ምግባራቱ ጀርባ ታዲያ ቅድስት እናቱ ነበረች።

ቅድስት እሌኒ ጾምን ጸሎትን ከማዘውተሯ ባሻገር አጽመ ሰማዕታትን ትሰበስብ፣ አብያተ ክርስቲያንን ታሳንጽ፣ ለነዳያንም ትራራ ነበር። በኢየሩሳሌምና አካባቢው ብቻ ከሰማንያ በላይ አብያተ መቃድስ አሳንጻለች። እነዚህንም በወርቅና በእንቁ ለብጣቸዋለች።

በዘመኗ መጨረሻም የጌታችንን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ ለዓለም በረከትን አስገኝታለች።

እናታችን ቅድስት እሌኒ እንዲህ በቅድስና ተመላልሳ በሰማንያ ዓመቷ በ፫፻፴ዎቹ አካባቢ ዐርፋለች። ቤተ ክርስቲያናችንም ስለ ቅድስናዋና ውለታዋ በዓል ሠርታ ታቦት ቀርፃ ስታከብራት ትኖራለች።

ከቅድስት እናታችን ምልጃና በረከት አምላካችን ያድለን።

ግንቦት ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት እሌኒ ንግሥት
፪.ቅዱስ ስልዋኖስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
፫.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
፬.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
፮.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

"ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ። የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።"
(ሮሜ ፲፮፥፲፱-፳)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራምም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ <3

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያህል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም።

ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ (በሦስት መቶ ዓ.ም አካባቢ) እስክንድርያ ግብጽ ውስጥ ነው የተወለደው። ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር።

ሕፃን እያለ ለጨዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ። ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት። አትናቴዎስም ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕፃናቱ ዕጣ ተጣጣሉ።

ለአንዱ ቄስ፣ ለአንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕፃናት ይሰግዱለት ጀመር። በአጋጣሚ ሕፃናቱ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕፃኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት።

ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ጳጳሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ የሚገባውን መንፈሳዊ ትምህርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት። ከዚህ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው። ምንም ሕፃን ቢሆንም ከሊቅነቱ፣ ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና።

ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት። በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው። ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ። ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው።

ከዚህ በኋላ የእስክንድርያ (የግብጽ) ሃያኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ። ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለአርባ ስምንት ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ። ለአምስት ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ አሳልፏል።

በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል። በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ) ይጠብቃቸው ነበር። ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚህ ዘመን የተጻፈ ነው።

በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን (ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ።

ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ። ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ያሳድድ ገባ። ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አትናቴዎስ ነበር።

በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ መናፍቅ ጳጳስ በግብጽ ሹሞ ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል ቅዱሱን ለስድስት ዓመታት አሰቃየው። የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግሥት ገብቶ ተናገረው።

ሁለት አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን፤ ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን) መልሰኝ።" አለው። መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ።

ቀዛፊ፣ መቅዘፊያ፣ ምግብና ውኃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው። ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ።

ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ ሌሎች መላእክት እየመገቡት እስክንድርያ(ግብጽ) አድርሰውት ተሠውረዋል። ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል።

ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በሦስት መቶ ሰባዎቹ ዓ.ም አካባቢ ዐርፏል።

ቤተ ክርስቲያን
ሊቀ ሊቃውንት፣
ርዕሰ ሊቃውንት፣
የቤተ ክርስቲያን /የምዕመናን/ ሐኪም (Doctor of the Church)፣
ሐዋርያዊ ብላ ታከብረዋለች።

አምላከ አበው ምሥጢራቸውን አይሰውርብን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ግንቦት ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፪.የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ (ጽንሰቱ)
፫.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ሃብቱን፣ ንብረቱን፣ ልብሱን ሳይቀር መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው)
፬.አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፬.አባ ባውላ ገዳማዊ
፭.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዓን ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ። ሐሴትንም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና።"
(ማቴ ፭፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራምም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ኤርምያስ <3

ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ከዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስድስት መቶ አካባቢ የነበረ ነቢይ ነው። አባቱ ኬልቅዩ ይባላል። ከካህናተ እስራኤል አንዱ ነበር።

እግዚአብሔር ኤርምያስን የጠራው ገና በሕፃንነቱ ነበር። "ከእናትህ ማኅጸን ሳትወጣ መርጬሃለሁ፤ ቀድሼሃለሁ።" ሲልም በገሃድ መስክሮለታል።
ኤር. ፩፥፭

ከቅዱሳን ነቢያት እንደ ኤርምያስ የተሰቃየና ያለቀሰ የለም። ከሰባ ዘመናት በላይ ስለ ወገኖቹ አልቅሷልና ሊቃውንት "ነቢየ ብካይ" (ባለ እንባው ነቢይ) ይሉታል።

ዘመኑ ዘመነ ኃጢአት (ዘመነ ዐጸባ) ነበር። እስራኤላውያን ከመሪዎቻቸው ከነ ሴዴቅያስ ጋር በክፋት ተባብረውም ነበርና ኤርምያስን አልሰሙትም። ይልቁኑ ክፉ ቦታ ውስጥ አስረው አሰቃዩት። እግዚአብሔር ግን በኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ አማካኝነት ከመከራው አዳነው።

የተሰበከላቸውን የንስሐ ጥሪ አልሰሙምና ስልምናሦር የሚባል የአሕዛብ ንጉሥ መጥቶ አሥሩን ነገድ ማርኮ በሰባት መቶ ሃያ ሁለት ዓመተ ዓለም አሦር (ነነዌ) አወረዳቸው በኋላ ደግሞ በኃይለኝነቱ የታወቀው የባቢሎን ንጉሥ ይማርካቸው ዘንድ ወደ ሁለቱ ነገድ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ኤርምያስ ወደ ከተማዋ ዳር ወጥቶ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቀሰ።

ከቤተ መቅደስ ንዋያት እኩሉን ለምድር አደራ ሰጣትና ሸሸገችው። ነቢዩ የተናገረው አይቀርምና ንጉሡ ናቡከደነጾር እኩሉን ገድሎ እኩሉንም ማርኮ ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ የአሕዛብ መዘባበቻ አድርጐ በአምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ዓለም ባቢሎን አወረዳቸው።

ቅዱስ ኤርምያስን ግን ትሩፋን (ከመከራው የተረፉት) ይዘውት ወደ ግብጽ ወረዱ እንጂ አልተማረከም።
በዚያም ተአምራትን አድርጐ አራዊትን አጥፍቷቸዋል። ትንሽ ቆይቶ ግን እውነተኛ አባት፣ ነቢይ፣ መምህርም ነውና ወደ ሕዝቡ (ወደ ባቢሎን) ወረደ። በዚያም ትንቢትን እየተናገረ ሕዝቡን ከሰባ ዓመታት በኋላ ወደ ሃገራቸው እንደሚመለሱ እያስተማራቸው በባቢሎን ቆይቷል። ያለ በደሉም በመከራቸው ተካፋይ ሆኗል።

ሰባው ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ በኤርምያስ መሪነት እስራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። አሁንም ግን ክፋታቸውን ይተው ዘንድ ፈቃደኞች አልነበሩምና ኤርምያስ ገሠጻቸው።

በዚህ ተበሳጭተው ሊወግሩት ሲሉ ጸጋ በዝቶለት ምሥጢርም ሰፍቶለት ስለ ነገረ ሥጋዌ (ስለ ክርስቶስ የማዳን ሥራ) አምልቶና አጉልቶ ትንቢት ተናገረ። አንዴ ልቡናቸው ታውሮ ኤርምያስ ነው ብለው ድንጋዩን በድንጋይ ሲወግሩት ውለዋል። ዘግይቶ ግን ኤርምያስ ራሱን ገለጠላቸው። ስለ እነርሱ ሲል ሰባ ዘመን ያለቀሰውንና ምትክ የሌለውን አባታቸውን ወግረው ገደሉት።

ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ሃምሳ ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት ተናግሯል (ጽፏል)። ዜና ሕይወቱ ከራሱ የትንቢት መጽሐፍ በተጨማሪ በተረፈ ኤርምያስ፣ በመጽሐፈ ባሮክ፣ በገድለ ኤርምያስ፣ በዜና ብፁዐን፣ በመጽሐፈ ስንክሳርም ተጽፏል።

ቸር እግዚአብሔር በኤርምያስ ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት ሕዝቦቿን ከስደትና ከመቅሰፍት ይሰውርልን።

ግንቦት ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ (ከታላላቆቹ ነቢያት አንዱ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
፫.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፭.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ

"ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ እንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።"
(ማቴ ፳፫፥፴፯-፴፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ያሶን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ <3

ባለንበት ዘመን አሳዛኝ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የቅዱሳኑ ስማቸው ከነሥራቸው መዘንጋቱ ነው። ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደማቸው እንዳልፈሰሰ አጥንታቸውም እንዳልተከሰከሰ ይሔው አስታዋሽ አጥተው ስማቸውም ተዘንግቶ ይኖራል።

አንዳንድ ንፉቃን ደግሞ ከዚሁ ብሶ ጭራሹኑ "ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስለ ክርስቶስ ትታ ስለ ቅዱሳኑ ብቻ ትሰብካለች።" ይሉናል።

በእጅጉ ከሚያሳዝኑኝ ነገሮች አንዱ የቅዱሳን ሐዋርያት (የመቶ ሃያው ቤተሰብ) መዘንጋት ነው። ከመቶ ሃያው ቤተሰብ የአብዛኞቹ ስም በመዘንጋቱ ሊቃውንቱም ዝምታን በመምረጣቸው "ያሶን፣ አርስጦስ፣ አፍሮዲጡ፣ ቆሮስ....." እያልን የሰባ ሁለቱን አርድእት ስም ስንጠራ ግር የሚለው ዓይነት ትውልድ ተፈጥሯል።

እስኪ እንዲያው ቢያንስ ሐዋርያትንና ዐበይት ቅዱሳንን እናስባቸው። አስበናቸው የሚጨመረልን እንጂ የሚጨመርላቸው የለምና።

ዛሬ የምናስበው ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ነው። ጌታችንን ከጥምቀቱ በኋላ ተከትሎ ለሦስት ዓመታት ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ ተምሯል። ከጌታችን ዕርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል።

ለብዙ ጊዜ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ተመላልሶ ሰብኳል። በመከራውም ተካፍሎታል። ታላላቆቹ ሐዋርያት ሰማዕትነትን ከተቀበሉ በኋላ ለመጣው አዲስ ክርስቲያን ትውልድ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በቃል የሰማውን አስተላልፏል።

ወንጌልን ስለ ሰበከላቸው አሕዛብ ብዙ ጊዜ አስረው ይደበድቡት ያንገላቱት ነበር። አንዳንድ ጊዜም እሳት እያነደዱ ያቃጥሉት ነበር። ፈጣሪው ግን በተአምራት እያዳነው ከእርሱ ጋር አልተለየም።

ከከተማ ወጥቶ በዱርና በእስር ቤቶች ብዙ ነፍሳትን ሽፍቶችንም ሳይቀር ወደ ክርስትና ማርኳል። ቅዱስ ያሶን ለረዥም ዓመታት ሰብኮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።

<3 ቡርክት ወለተ ማርያም <3

ዳግመኛ በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊቷ እናታችን ቡርክት ወለተ ማርያም ትታሰባለች።
ወለተ ማርያም ማለት የደጉ አፄ ናኦድ ሚስት የአፄ ልብነ ድንግልና የቅድስት ሮማነ ወርቅ እናት ናት። በንግሥትነት በቆየችባቸው ዘመናት (ከ፲፬፻፹፯-፲፭፻ ዓ.ም) የረሃብ ጊዜ በመሆኑ ብዙ ሕዝብ አልቆ ነበር።

ቡርክት ወለተ ማርያም ከጾምና ከጸሎት ባሻገር የተራቡትን በማብላት ብዙዎችን ታድጋለች። የንጉሡን ቤተሰብ ወደ መልካም ክርስትና በመምራትም የተመሰገነች ነበረች። በዚህች ዕለትም ዐርፋ ተቀብራለች::

አምላካችን ከቅዱሳኑ በረከት አይለየን።

ግንቦት ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ)
፪.አባ ብሶይ ሰማዕት
፫.ቅዱስ አውሳብዮስ ቀሲስ
፬.ቡርክት ወለተ ማርያም ንግሥት (የዐፄ ልብነ ድንግል እናት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
፬.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭.አቡነ ዜና ማርቆስ
፮.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

"ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው ጌታ ሆይ! አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። እንዲህም አላቸው..... እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ። የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ። ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።"
(ሉቃ ፲፥፲፯-፳)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ሰላም ዕብል ለልደትኪ ማኅቶት፣
ዘብሔረ ጽልመት፣
አእሚሮሙ ብኪ ከመ ትከውን ሕይወት፣
ሰመዩኪ ማርያም ዘወለዱኪ ነቢያት፣
ዘትርጓሜሁ ጸጋ ወዓዲ እግዝእት።"
(ለጨለማው ዓለም ብርሃን የፈነጠቅሽለት ማርያም ሆይ ለልደትሽ ምስጋና አቀርባለሁ። ልደትሽን ሰላም ብዬ እጅ እነሣዋለሁ። አባቶችሽ ነቢያት ማርያም ብለው ስም አውጥተውልሻልና። ትርጓሜውም እመቤት አንድም ጸጋ ወሀብት ማለት ነው።)
(አርኬ ዘግንቦት ፩)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ።"
መኃ ፬፥፰
እንኳን ለእመ አምላክ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

እንዲህ ኃጢአታችን ጽዋዑን ሞልቶ በተረፈበት በዚህ ዘመን አንዲት ሰዓትም ውድ የሆነች የንስሐ ዕድሜ ናት። እግዚአብሔር ግን ደግ ነውና ይሔው ሚያዝያን አስፈጸመን።

ባይገባን ነው እንጂ በዚህች ወር ውስጥ ሚሊየኖች በደዌ የአልጋ ቁራኛ ሁነዋል።
ሚሊየኖችም ለንስሐ ሳይበቁ እንዲሁ አንቀላፍተዋል (ሙተዋል)።

እስኪ እርሱ አምላካችን ቀሪዋን ዘመን ደግሞ ለንስሐና ለመልካም ሥራ ባርኮ ይስጠን።

<3 ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ <3

በዚህች ዕለት፦
ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነ
ወንጌላዊ፣
ሐዋርያ፣
ሰማዕት፣
ዘአንበሳና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተባለ ቅዱስ ማርቆስ በሰማዕትነት ግብጽ ውስጥ ዐርፏል።

ቅዱስ ማርቆስ እናቱ ማርያም አባቱ አርስጥቦሎስ ይባላሉ። በልጅነቱ ኦሪትንና የዘመኑን ጥበብ ሥጋዊ በሚገባ ተምሮ ክርስቶስን ከቤተሰቦቹ ጋር ተከትሏል።

የመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን ከመቶ ሃያው ቤተሰብ በእድሜ በጣም ትንሹ (ሃያ ዓመት) እርሱ ነበር። ለሦስት ዓመታት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ ደክሟል።

በተለይ የግብጽና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው። ክህነትን ያገኘን ከእርሱ ነውና። ቅዱስ ማርቆስ አሥራ ስድስት ምዕራፍ ያለውን ወንጌሉን ሲጽፍ ኪሩብ ገጸ አንበሳ በቀኙ ሊቀ ሐዋርያት በግራው ሆነው ይራዱት ነበር።

ቅዱሱ ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ከበርናባስና ጴጥሮስ ጋር ተጉዟል። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ሰሜን አፍሪካ አካባቢ በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውታል።

ዳግመኛ በዚህች ቀን የቅዱስ ማርቆስን ወላጆችን እናስባቸው ዘንድ ይገባል።
ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ) የጌታ ቅን አገልጋይ የነበረ፤
ቅድስት ማርያም (እናቱ)
ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ፣
ጌታችንን ያገለገለች፣
ቤቷን ለሐዋርያትና ለጌታ በስጦታ ያበረከተች ቅድስት ናት።
ቤቷም (ጽርሐ ጽዮን) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ይህች ቤት መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል። የእመቤታችን ግንዘትም ተከናውኖባታል።

እግዚአብሔር ከሐዋርያዊው ቅዱስ ቤተሰብ በረከትን ያድለን።

ሚያዝያ ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ)
፫.ቅድስት ማርያም (እናቱ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.አባ ሣሉሲ ክቡር
፫.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

".....እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሏት አንዲት አገልጋይ ትሰማ ዘንድ ቀረበች። የጴጥሮስ ድምጽ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሳ ደጁን አልከፈተችም። ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች።"
(ሐዋ ፲፪፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ ወሰማዕት አባ ሜልዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። 
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! 
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it) 
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ 
 
<3 ሜልዮስ ሰማዕት <3 
 
ቅዱስ ሜልዮስ ልጅነቱን በመንፈሳዊ ትምህርት ያሳለፈ በጉብዝናው ወራት ፈጣሪውን ያሰበ ደግ ክርስቲያን ነው። ይህችን ዓለም ከነ ክፋቷ ንቆ ኮራሳት ወደሚባል በርሃ ሔዶ በተራራውና በደኑ ውስጥ በጾምና በጸሎት በትሕርምትም ለበርካታ ዓመታት ተጋድሏል። 
 
በእነዚህ የብሕትውና ዘመናቱ ልብሱን ፀሐይና ብርድ ቆራርጦ ስለ ጨረሳቸው ፈጣሪው ጸጉርን አልብሶታል። የአባ ሜልዮስ ጸጉሩ እስከ እግሩ ጽሕሙ እስከ ጉልበቱ ነበር። 
 
እድሜው ገፍቶ ሲያረጅ እንዲያገለግሉት እግዚአብሔር ሁለት ወጣት ምስጉን ክርስቲያኖችን ላከለት። እነርሱም አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ ይባላሉ። ሁለቱ ቅዱሳን አምላካቸውን እግዚአብሔርንና አባታቸው ቅዱስ ሜልዮስን በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል። 
 
ከቆይታ በኋላ ግን በአካባቢው የነበሩ ጣዖት አምላኪዎች አራዊት እናጠምዳለን ብለው በዘረጉት መረብ ቅዱስ ሜልዮስን ያዙት። ክርስቲያን መሆኑን ሲያውቁ "ለፀሐይ ስገድ።" ብለው ደበደቡት። 
 
ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው መጥተው አባታቸውን በመከራ መሰሉት። ክርስቶስን አንክድም ስላሉ ሁለቱንም በሰይፍ አንገታቸውን መቷቸው። ቅዱስ ሜልዮስን ግን ለአሥራ አምስት ቀናት ካሰቃዩት በኋላ በዚህች ቀን በቀስት በተደጋጋሚ ወግተው ገድለውታል። ጻድቅና ሰማዕት ቅዱስ ሜልዮስ ብዙ ተአምራትን አድርጓል። 
 
ገዳዮች ግን ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ የሜዳ አህያ ሊያድኑ የወረወሩትን ቀስት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እነርሱ መልሶባቸው ልብ ልባቸውን ተወግተው ሙተዋል። 
 
ቸሩ አምላካችን ከቅዱስ ሜልዮስና ከደቀ መዛሙርቱ በረከትን ያካፍለን። 
 
ሚያዝያ ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 
፩.ቅዱስ ሜልዮስ ዘደብረ ኮራሳን (ጻድቅና ሰማዕት) 
፪.አባ ኢያሱና አባ ዮሴፍ (ደቀ መዛሙርቱ) 
፫.ቅዱስ ብስጣውሮስ ሰማዕት (ተንባላት የገደሉት) 
 
ወርኀዊ በዓላት 
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን 
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ) 
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ 
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ 
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት) 
 
"ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው። አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን። የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።" 
(ራእይ ፪፥፲) 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ።"
(ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሰማዕታቱ ቅዱስ ዮሐንስ ወቅዱስ ሱስንዮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሰማዕቱ ቅዱስ ዮሐንስ <3

ቅዱስ ዮሐንስ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ቅዱስ ሰው ነው። ወላጅ አባቱ ጣኦት ጠራቢና አምላኪ የጣኦቱ አጣኝም ነበረ። እናቱ ግን በድብቅ ክርስቶስን ታመልክ ነበር።

ልጇን ክርስትና ብታስተምረው አባቱ ጨካኝ በመሆኑ ይገድለዋልና ዘወትር ጧት ማታ ወደ ፈጣሪዋ በዕንባ ትለምን ነበር። ጧት ጧት አባቱ ጣኦት መጥረብና ማምለክን ያስተምረው ነበር። አንድ ቀን እግዚአብሔር ለሕፃኑ ዮሐንስ በራእዩ ተገለጠለት። ምሥጢራትንም አስተማረው።

ለተወሰነ ጊዜ በሚደነቅ የክርስትና ሕይወት ከኖረ በኋላ ገና እድሜው አሥራ ሁለት ዓመት ቢሆንም አባቱን "ጣኦትህን ተው።" ሲል መከረው። አባቱ ግን ጨካኝ ነውና ትልቅ መጥረቢያ አንስቶ አንገቱን መታው። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ መሬት ላይ ስትወድቅ አካሉ ግን ለአንድ ሰዓት ቆሞ በደሙ ተጠመቀ። ይህ ሁሉ ሲሆን የተባረከች እናቱ ቆማ ታይ ነበር።

መንፈሳዊት እናት ናትና አላዘነችም። ይልቁኑ ከልጇ ደም ለበረከት ተቀባች። አለችም፦ "ጌታ ሆይ! የምሰጥህ ምንም የለኝም። ይህንን ንጹሕ መስዋዕት ግን ተቀበለኝ።"

ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ካለፈ በኋላ አባቱን ርኩሳን መናፍስት አሳበዱት። እናት ግን አረማዊ ባለቤቷን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መቃብር ወስዳ ጸለየች። "ልጄ ሆይ! አባትህን ይቅር ብለህ ከፈጣሪ ዘንድ አማልድ።"
ይህንን ብላ ባሏን ከመቃብሩ አፈር ወስዳ ቀባችው። አባትም በቅጽበት ድኖ ወደ ልቡ ተመለሰ። ስለ ሠራው ሁሉ ተጸጽቶ አለቀሰ። በእውነተኛ አምላክ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቆ በመልካም ክርስትና ኑሮ ከተባረከች ባለቤቱ ጋር ለገነት በቅቷል።

<3 ቅዱስ ሱስንዮስ <3

ዳግመኛ በዚህች ቀን ቅዱስ ሱስንዮስ ተሰይፏል። ቅዱሱ በዘመነ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያንን በገድላቸው ካስጌጧት ታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ከሰማዕታቱ ጽናትን ጸጋ በረከትን ይክፈለን።

ሚያዝያ ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት (ወልደ ፀራቢ)
፪.ቅዱስ ሱስንዮስ ሰማዕት (ሶርያዊ)
፫.አንድ ሺህ አንድ መቶ ዘጠኝ ሰማዕታት (የቅዱስ ሱስንዮስ ማኅበር)
፬.አባ ሠርጋ
፭.ቅዱስ ይድራስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"ሰውን ከአባቱ ሴት ልጅንም ከእናቷ ምራትንም ከአማቷ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና። ለሰውም ቤተሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።"
(ማቴ ፲፥፴፭-፴፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ፃና ሰማዕት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ፃና <3

በቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን አሉ።
ዛሬ የምናከብረው ሰማዕቱ ቅዱስ ፃና
በዘመነ ሰማዕታት የነበረ፣
ቅዱስ ኤስድሮስ የሚባል ደግ ጓደኛ የነበረው፣
ሁለቱንም እናቶቻቸው እንደሚገባ ያሳደጓቸው የሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ነበሩ።

በወጣትነት ዘመናቸው በድንግልና ቅዱስ ፃና የሠራዊት አለቃ ቅዱስ ኤስድሮስ ደግሞ የልብስ ዝግጅት ባለሙያ ነበሩ። ከሚያገኙት ገቢ ለዕለት ጉርስ ብቻ እያስቀሩ ለነዳያን ይመጸውቱ ነበር።

በመከራ ዘመን (ዘመነ ሰማዕታት) ቅዱሳኑ ያላቸውን ሁሉ ለነዳያን አካፍለው በክርስቶስ ስም መሞትን መርጠዋል። አስቀድሞ ቅዱስ ኤስድሮስ አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀዳጅቷል።

ሰማዕቱ ቅዱስ ፃና ባልንጀራው ኤስድሮስ ከተገደለ በኋላ ለሠላሳ ስድስት ቀናት በጨለማ እሥር ቤት ውስጥ ከብዙ ስቃይ ጋር ቆይቷል። መከራን ቢያፀኑበትም በሃይማኖቱ ጽኑ ነበርና እርሱንም በዚህች ቀን ገድለውታል።

ደግ እናቱ በቦታው ነበረችና መላእክት በክብር ነፍሱን ሲያሳርጉ ተመልክታለች።

ፈጣሪ ከሰማዕቱ ክብር ያድለን።

ሚያዝያ ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፃና ሰማዕት
፪.አባ ሱንቱዩ ሊቀ ጳጳሳት
፫.አባ ይድራ
፬.የደብረ ሲና ቅዳሴ ቤት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤጲስ ቆጶስ)
፫.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
፭.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፮.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፯.ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል)
፰.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)

"ልጆች ሆይ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ አሸንፋችኋቸውማል። በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። እነርሱ ከዓለም ናቸው። ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ። ዓለሙም ይሰማቸዋል። እኛ ከእግዚአብሔር ነን። እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል። ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም።"
(፩ዮሐ ፬፥፬-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሚያዝያ 23፦ ጸሎቱና በረከቱ ለሁላችን ይደረግልንና ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው ተአምር ይህ ነው።

ብባ ከምትባል አገር ሰዎች ወገን የሆነ አንድ አረማዊ ሰው ነበረ፡፡ መካ የሚገኘውን መስጊድ ለመጎብኘት ወደ ምድረ ኅልዛዝ ሔደ፡፡ በዚህም ቦታ ዲያብሎስ ከነሠራዊቱ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀበት ነው፡፡ ዳግመኛም የአትሪብን አገር ነቢይ መቃብር ይጎበኝ ዘንድ ሔደ፡፡ ጉብኝቱንም ከፈጸመ በኋላ ከጓደኞቹ ጋር ወደ ሀገሩ ተመልሶ እየሔደ ሣለ ወደኋላ ዘግይቶ ቆየና በዱር ብቻውን ቀረ፡፡ መሪር ልቅሶንም አለቀሰ፡፡ ምድሪቱም በጣም በረሃ ናትና ምንም የለባትም፣ ይልቁንም የዘላን ወይም የሽፍታ መኖሪያ ነበረች፡፡ አረማዊውም ወደ ነቢያቸውና ወደ ጓደኞቹ ቢጮህ ማንም ለእርዳታ የሚደርስለት አላገኘም፡፡ በዚህም ጊዜ በጭንቅና በፍርሃት ሆኖ በመከራ ጊዜ ስሙ ሲጠራ ይሰማው የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስን ስም እየጠራ እንዲረዳው እየጮኸ ለመነ፡፡ ወዲያውም ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ መጥቶ በፈረሱ ላይ አፈናጠጠውና እንደ ዓይን ጥቅሻ ፈጥኖ ብባ ከምትባለው ሀገሩ አደረሰውና ከእርሱ ተሰወረ፡፡

የመጣበትም ሀገር ጎዳና ሦስት ወር ያህል የሚያስኬድ ነበር፡፡ ሰውየውም ይህን ታላቅ ተአምር ከተመለከተ በኋላ ልቡ ተሰወረ፣ እንደሕማም ሆነበት፡፡ አእምሮውንም ካወቀ በኋላ ግን ተነሥቶ ወደ ቤቱ ገባ፡፡
የሀገሩ ሰዎችም ‹‹ሌሎቹ ሰዎች ወይም ጓደኞችህ ከመምጣታቸው በፊት ከዚያ ከሩቅ አገር አንተ ብቻህን እንዴት መጣህ?›› ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፈረሱ ላይ አፈናጦ በቅጽበት ወደ ሀገሩ እንዳመጣው ነገራቸውና ምልክትም ትሆነው ዘንድ ከመካ ያመጣትን ከሸክላ የተሠራችና የሰጎን እንቁላል የምትመስል ነገር አሳያቸው፡፡ እነርሱም በሰሙት ነገር እጅግ ተደነቁ፡፡ ሰውየውም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይዞ ሔዶ ያችን ምልክት ለኤጲስ ቆጶሱ ሰጠውና ኃያሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገለትን እርዳታ ከሩቅ አገር እንዴት አድርጎ እንደ ዓይን ጥቅሻ በቅጽበት እንዳመጣው ነገረው፡፡ እስከ መጨረሻውም ድረስ ለዚህ ተአምር መታሰቢያ ሆኖ ይኖር ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ይሰቅለው ዘንድ ለመነው፡፡ ኤጲስ ቆጶሱም በቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል አንጻር መጻሕፍት እንደሚነበቡባቸው ያለ ከፍተኛ ቦታ ላይ አስቀመጣት፡፡ በወቅቱም የቅዱስ ጊዮርጊስን ገድል የጻፈው ሰውም ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ያችን ምልክት እንዳያት በጻፈው የሰማዕቱ ገድል ላይ ጠቅሶታል፡፡ ያች እንቁላል መሰል ሸክላ በመካ ሀገር ከሚገኝ መስጊድ በስተቀር ሌላ የትም ቦታ ላይ አትሰቀልም ነበር፡፡ የገድሉ ጸሐፊም ይህን ጠቅሶ ኤጲስ ቆጶሱን እንዴት ይህችን ሸክላ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሰቀሏት ጠየቀው፡፡ ኤጲስ ቆጶሱም ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአረማዊው ያደረገለትን ተአምር ከምድረ አልኅዛዝ በፈረሱ ላይ አፈናጦ እንደ ዓይን ጥቅሻ ወደ ሀገሩ በማምጣት ከሞት እንዳዳነው ነገረው፡፡ ያችንም እንቁላል መሰል ሸክላ በመታሰቢያ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ እንዲሰቅልለት አረማዊው እንደለመነው ነገረው፡፡
የገድሉ ጸሐፊም በቅዱሳን አድሮ ድንቅ ድንቅ ነገርን የሚሠራ ልዑል እግዚአብሔርን እያመሰገነ ታሪኩን ከገድሉ ጋር ጻፈው፡፡

የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎቱ በረከቱ ለሁላችን በዕውነት ይደረግልን አሜን!

ዳግመኛም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዚያ አረማዊ ሰው ታላቅ ተአምር ባደረገባት በዚያች ብባ በምትባል አገር የሚኖር አንድ አረማዊ ነበር፡፡ እርሱም ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚወድ በየዓመቱም በዕረፍቱ ዕለት ሚያዝያ 23 ቀን ብዙ በግና ፍየል እያረደ ዝክሩን የሚዘክር ነው፡፡ ለበዓሉም የሚያስፈልጉትን ሁሉ እያዘጋጀ ያቀርባል፡፡ በሥራውም ሁሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ ይታመናልና ስለዚህም ነገር አረማውያን ጓደኞቹ ቀኑበት፡፡ ክርስቲያኖችን ወደሚጠላው አገረ ገዥ ዘንድ ሔደው የቅዱስ ጊዮርጊስን በዓልም እንዳያደርግ ከሦስት ቀን በፊት ከሰሱት፡፡ ገዥውም ፈጽሞ በመቆጣት ደብዳቤ ጻፈና አትሞ አሽጎ ለዚያ የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ለሚያዘክር አረማዊ ሰው ሰጠውና እልቅሐራ ወደምትባል ሩቅ አገር ደብዳቤውን በፍጥነት ወስዶ በዚያ ላለው ገዥ ይሰጥ ዘንድ አዘዘው፡፡ እንዲከታተሉትም ወታደሮችን አብረው እንዲሔዱ አዘዘ፡፡ ይህንንም ያደረገው በዓሉን እንዳያደርግ ሊያስታጉለው ፈልጎ ነው፡፡

ያ አረማዊና ጭፍሮቹም መጓዝ ጀምረው ከከተማው ውጭ እየሔዱ ሣሉ አረማዊው ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! የበዓልህን መታጎል ተመልከት›› እያለ ጸለየ፡፡ ወዲያውም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ተገለጠለትና ‹‹አይዞህ አትፍራ ና›› ብሎ እጁን ይዞ ከፈረሱ ላይ አስቀመጠውና እንደ ዓይን ጥቅሻ በቅጽበት ወስዶ ገዥው ካዘዘበት እልቅሐራ አገር ከገዥው ደጃፍ አደረሰው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሒድ ግባ የተላከውን ደብዳቤ አድርስ፣ መልሱንም ጽፎ ይሰጥሃል፣ እኔም እስክትመለስ ድረስ ከዚህ ቆሜ እጠብቅሃለሁ›› ብሎ ላከው፡፡
ገዥውም የተጻፈለትን ደብዳቤ ካነበበ በኋላ መልሱን ጽፎ ሰጠው፡፡ እርሱም ፈጥኖ ወደውጭ ቢወጣ ቅዱስ ጊዮርጊስን በፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ እየጠበቀው አገኘውና እጅግ ደስ አለው፡፡ ሰማዕቱም ዳግመኛ ከፈረሱ ላይ አፈናጠጠውና በቅጽበት አረማዊውን ወደመጣበት አገር አደረሰውና ‹‹ወደ ቤትህ ግባና እንደ ልማድህ የበዓሌን መታሰቢያ አድርግ›› አለው፡፡ ያም አረማዊ ሰው በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝቶ ወደ ቤቱ ሔዶ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከቀድሞ አስበልጦ አዘጋጀና ወስዶ ለኤጲስ ቆጶሱ ሰጠው፡፡
እነዚያ መጀመሪያ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን በዓል እንዳያደርግ ለማስታጎል ብለው የከሰሱት አረማውያን ሰዎችም ዳግመኛ ወደ ገዥው ዘንድ ሔደው ‹‹እነሆ ያ ወደ ሩቅ ሀገር ደብዳቤ ይዞ እንዲሔድ ያዘዝከው ሰው በአንተ ላይ ተዘባበተብህ፣ ሳይሔድ ቀርቶ እርሱ ግን የጊዮርጊስን በዓል ለማክበር ይዘጋጃል›› ብለው ዳግመኛ ከሰሱት፡፡ ገዥውም እጅግ ተናዶ አስመጥቶ ጠየቀው፡፡ ሰውየውም ‹‹ጌታዬ ወደላከኝ አገር መልእክትህን አድርሻለሁ፣ የመልእክትህም መልስ እነሆ›› ብሎ የመልሱን ደብዳቤ ሰጠው፡፡ ገዥውም የመልሱን ደብዳቤ ባነበበው ጊዜ እርሱ ጽፎ በላከበት ዕለት የተጻፈ ደብዳቤ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ በዚህም እጅግ ተገርሞ ‹‹ይህ መንገድ ለሦስት ቀን ያህል የሚያስኬድ በጣም ሩቅ አገር ሆኖ ሳለ አንተ እንዴት በቅጽበት ደረስህ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ሰውየውም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገለትን ድንቅ ነገር በዝርዝር ነገረው፡፡ እነዚያ አብረውት ይሔዱ ዘንድ የተላኩት ጭፍችሮችም ከስድስት ቀን በኋላ ተመልሰው መጥተው አረማዊው ከእነርሱ በዕለቱ ተለይቶ እንደነበር እነርሱ ግን ወደታዘዙበት አገር ደርሰው እንደመጡ ተናገሩ፡፡ አገረ ገዥውም ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታላቅ ተአምርና ገናናነት ፍርሃት አደረበት የሚቀስፈው መስሎታልና፡፡ የአገሩ ሰዎችም ሁሉ በተደረገው ታላቅ ተአምር ተደንቀው ፍርሃት አደረባቸው፡፡ ገዥውም ኤጲስ ቆጶሱን ጠርቶ ሁልጊዜም በየዓመቱ የቅዱስ ጊዮርጊስን በዓል ማክበሪያ የሚሆን ብዙ ገንዘብና ለበዓሉ ዝግጅት አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ አሟልቶ ለቤተ ክርስቲያኑ ሰጠ፡፡

መልእክተኛውን ሰው ጌታው ወደ ንጉሡ አስተዳደር በላከው ጊዜ ሦስት ቀን የሚያስኬደውን ሩቅ መንገድ በቅጽበት አድርሰህ የመለስከው ኃያሉ ሰማዕት ፀሐይ ዘልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! እኛንም በአማላጅነትህ የምንታመን ልጆችህን ከርኩሰት የበደል ጎዳና በረድኤትህ መልሰን!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ <3

<3 ልደት <3
መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው። እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ፣ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል።

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል። በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል።

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ ቀን በ፲፪፻፮ ዓ.ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን በ፲፪፻፯ ዓ.ም ነው። በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል። ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል።

<3 ዕድገት <3
የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል። ይህንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል። በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት፣ ሐዲሳትን) ተምረዋል። በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል። ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል።

<3 መጠራት <3
አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ።

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ። "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን። ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ። ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በግርማ ዐረገ። ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም። ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ።

<3 አገልግሎት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ። በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ሁለት መልክ ነበራት።
፩ኛ.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል።
፪ኛው. ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር።

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ። ሕዝቡንና መሳፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል።

<3 ገዳማዊ ሕይወት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል። እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በሦስት ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል።

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለአሥራ ሁለት ዓመታት፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለሰባት ዓመታት፣ በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለሰባት ዓመታት በአጠቃላይ ለሃያ ስድስት ዓመታት አገልግለዋል።

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለሃያ ሁለት ዓመታት ቆመው ጸልየዋል። በተሰበረ እግራቸውም ስድስት ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለሰባት ዓመታት ጸልየዋል።

<3 ስድስት ክንፍ <3
ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል። ጻድቁ ምድረ እስራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ፣ እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር።

የወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው። ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር።

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም። በገሃድ፦
በቤተ መቅደስ ብስራቱን፣
በቤተ ልሔም ልደቱን፣
በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣
በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣
በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር።

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ።
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አባታችንን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው።

በዚያም፦
የብርሃን ዓይን ተቀብለው፣
ስድስት ክንፍ አብቅለው፣
የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣
ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣
ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው፣
ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል።

<3 ተአምራት <3
የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው።
ሙት አንስተዋል፣
ድውያንን ፈውሰዋል፣
አጋንንትን አሳደዋል፣
እሳትን ጨብጠዋል፣
በክንፍ በረዋል፣
ደመናን ዙፋን አድርገዋል።

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል። በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል። በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና።

<3 ዕረፍት <3
ጻድቅ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው፣ መከራን በብዙ ተቀብለው፣ እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ ቀን በ፲፫፻፮ ዓ/ም ዐርፈዋል። ጌታ፣ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል። አሥር ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል።

የተክለ ሃይማኖት አምላክ ከጻድቁ ትሩፋት፣ ጸጋና በረከት ይክፈለን።

ሚያዝያ ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (አርዮስን ያወገዘ)
፫.አባ ይስሐቅ ጻድቅ
፬.አባ ማርቆስ ሐዲስ
፭.አባ ሚካኤል ዘኢየሩሳሌም
፮.አባ ሚካኤል ዘእስክንድርያ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፬.አባ እንጦንዮስ (አበ መነኮሳት)
፭.አባ ጳውሊ የዋህ

"ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት። የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌል ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር። ለእያንዳንዱ ስድስት ክንፍ ነበረው። በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር። በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር። በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ 'ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች።' እያለ ይጮህ ነበር።"
(ኢሳ ፮፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…
Subscribe to a channel