እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ <3
ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በሦስት ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል።
እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ ያሉት በሃያዎቹ ውስጥ፣ ቅዱስ ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በሠላሳና በአርባዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን እነ ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ በሃምሳዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ። ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም፣ ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው።
ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) ስምዖን እና ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል።
ቅዱሱ ጌታችንን ተከትሎ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ፣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ እግር ተምሮ፣ በዕርገቱ ተባርኮ፣ በበዓለ ሃምሳም ሰባ አንድ ልሳናትን ተቀብሎ፣ ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል።
ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ። ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው። ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን።" አሉት። እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሔደ።
ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም።" አለው። ሁለቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር፣ ጴጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ። ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ፣ አፍርቶ፣ እሸት ሆኖ ቆየው።
ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ። ሊያመልካቸውም ወደደ። እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን።" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት። "ልከተላችሁ?" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን። እኛ እንመጣለን።" አሉት።
እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ። ተሠብስበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም።" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ።
ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ ቅዱስ ሚካኤልን "እርዳን" አለው። ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት። በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ። ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው።
አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ።" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር። ያን ጊዜ "ጌታዬ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል። ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት ሦስት ጊዜ አሳልፎታል።
ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል።" (ማር. ፲፥፳፫)
በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ። ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ። ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግሥትን ስበክ።" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል።
ቅዱሳኑ ታዴዎስና ጴጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው፣ ካህናትን ሹመው፣ ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል።
ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል። ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል። ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በኋላም በዚህች ቀን ዐርፏል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን።
ሐምሌ ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
፭.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፮.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
"ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።" አላቸው።"
(ማር ፲፥፳፫-፳፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ <3
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል።
"ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ።" ይላቸዋል።
(ሉቃ. ፩፥፮)
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና (ሰባ አምስት) የዘካርያስ ደግሞ መቶ (ዘጠና) ደርሶ ነበር። ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተእርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ፣ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው።
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች። በስድስተኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ በዚህች ቀን (ሰኔ ፴) ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፦
የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ፣
በማኅጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፣
በበርሃ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ፣
እስራኤልን ለንስሐ ያጠመቀ፣
የጌታችንን መንገድ የጠረገ፣
ጌታውን ያጠመቀና
ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው።
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን፦
ነቢይ፣
ሐዋርያ፣
ሰማዕት፣
ጻድቅ፣
ገዳማዊ፣
መጥምቀ መለኮት፣
ጸያሔ ፍኖት፣
ቃለ ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች።
<3 አባ ጌራን ሕንዳዊ <3
ዳግመኛ በዚህች ቀን ሕንድ ካፈራቻቸው ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት ጻድቁ አባ ጌራን ይታሰባሉ። የእኒህ ቅዱስ ታሪክ አሳዛኝ ነው። ቅዱሱ በሕንድ ተወልደው፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድገው፣ ገና በወጣትነታቸው መንነው፣ ደሴት ውስጥ ወደሚገኝ አንድ በርሃ ገብተዋል።
ከገድላቸው ጽናት ከቅድስናቸውም ብዛት የተነሳ በሃገረ ሕንድ ሰይጣን እንዳይገባ፣ ጠብ ክርክር እንዲጠፋና ሰው ሁሉ በፍቅርና በሰላም እንዲኖር ማድረግ ችለው በጣም ተወዳጅ ነበሩ።
በዚህ የተበሳጨ ሰይጣን ግን ባልጠረጠሩት መንገድ መጣባቸው። አንዲት ሴት ወደ እርሳቸው መጥታ (የንጉሡ ልጅ ነኝ በሚል) አስጠግተዋት ነበር። አንድ ሌሊት ላይ ግን አውሬ ያባረራት በመምሰል ሩጣ ወደ ቤታቸው ገብታ አቀፈቻቸው። በዚያች ቅጽበት ፍጡር ደካማ ነውና ታላቁ አባ ጌራን ተሰነካከሉ። ከአፍታ በኋላ የሆነውን ሲያውቁ ደም አለቀሱ።
ልብሳቸውን ቀደው እንባቸው እንደ ዥረት እየፈሰሰ አለቀሱ። ራሳቸውን በትልቅ ድንጋይ እየቀጠቀጡት የጭንቅላታቸውና የደረታቸው አጥንቶች ተሰባበሩ። እርሱ እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ይቅር ብሎ የቅድስና ስም ሰጥቶ በዚህች ቀን ወደ ገነት አሳርጓቸዋል። ለዚህ ነው መጽሐፉ "ስብአ ይወድቅ ጻድቅ ወስብአ ይትነሣእ - ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፤ ይነሣማል።" ያለው።
(ምሳ. ፳፬፥፲፮)
አምላካችን ከቅዱሱ ቤተሰብና ከጻድቁ አባ ጌራን በረከት ይክፈለን።
ሰኔ ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት (ልደቱ)
፪.ቅዱሳን ዘካርያስና ኤልሳቤጥ (ወላጆቹ)
፫.አባ ጌራን መስተጋድል (ሕንዳዊ)
፬.ቅዱሳት ደናግል ማርያና ማርታ (ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
፪.አባ ሣሉሲ ክቡር
፫.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
"ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ። መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና። እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ። ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው።"
(ሉቃ ፩፥፸፮-፸፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለስደተኛው ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎዶስዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አባ ቴዎዶስዮስ <3
ጻድቁ ሊቀ ጳጳሳት ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ከልጅነቱ መጻሕፍትን ተምሮ በመንኖ ጥሪት የሚኖር ደግ ሰው ነበር። ያ ዘመን መለካውያንና ልዮናውያን (ክርስቶስን ሁለት ባሕርይ የሚሉ) የሰለጠኑበት ዘመን ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ተዋሕዶን የሚያምኑ ሊቃውንትና ምዕመናን ቁጥራቸው የተመናመነ ነበር።
ችግሩ ግን ይህ ብቻ አልነበረም። በጊዜው ተዋሕዶን አምኖ መገኘት እስከ ሞት የሚደርስ ዋጋንም ያስከፍል ነበር። ለዚህም ነው ሮማውያን ሃይማኖትን በግድ ለማስለወጥ ከነገሥታቱ ጋር የተቆራኙት። ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጋግራ ደሴት ውስጥ ከተገደለ በኋላ በግብጽ የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት አብዛኞቹ መከራና ስደትን ቀምሰዋል። ትልቁን ቦታ ግን አባ ቴዎዶስዮስ ይወስዳል።
አባ ቴዎዶስዮስ ለእስክንድርያ (ግብጽ) ሠላሳ ሦስተኛ ፓትርያርክ ነው። እረኝነት (ጵጵስና) እንዳሁኑ ዘመን ሠርግና ምላሽ አይደለምና ገና እንደ ተሾመ የቀረበለት ጥያቄ አንድ ነበር። "ተዋሕዶን ትተህ መለካዊ ትሆናለህ ወይስ የሚከተልብህን ፍርድ ትቀበላለህ?" አሉት። ይህንን ያሉት ከንጉሡ ዮስጢያኖስ የመጡ መልእክተኞች ነበሩ። መልሱ ፈጣን ሆነባቸው። "እኔንም ሆነ ሕዝቤን ከቀናችው እምነታችን በምንም ልትለዩን አትችሉም።" አላቸው።
በዚህ ምክንያት በቀጥታ ግዞት (ስደት) ተፈረደበት። ወደ በርሃ ሲያግዙት ካህናትን፣ መምህራንንና ምዕመናንን አደራ ብሏቸው ሔደ። መናፍቃኑ እርሱን ካሰደዱ በኋላ ሕዝቡን ለመቀየር ብዙ ደክመዋል። ግን ሊሳካላቸው አልቻለም። ምክንያቱም አደራነትን የማይረሱ ደጋግ መምህራን ነበሩና ነው።
በዚያ ላይ አባ ቴዎዶስዮስ ጦማር (መልእክት) በየጊዜው ይጽፍላቸው ነበር። እጅግ ብዙ ከሆኑት መልእክቶቹ የተወሰኑት ዛሬም ድረስ ሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ።
በዚህ አስቸጋሪ ዘመን መልካም ነገሮችም ነበሩ። ቀዳሚው ማኅቶተ ተዋሕዶ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የንጉሡ ሚስት የተባረከችው ታኦድራ ናት።
አባ ቴዎዶስዮስ በግዞትና በስደት ሳለ ንግሥቲቱ ትራዳው ምዕመናንንም ትንከባከብ ነበር። ቅዱስ ያዕቆብ ከሊቀ ጳጳሱ ዘንድ ክህነትን ተቀብሎ ከሶርያ እስከ ምድረ ግብጽ ስለ ተዋሕዶ ሕልውና ተጋድሏል። ምናልባትም ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኋላ በፈሊጥ ክርስትናን በማስፋፋት ቀዳሚ አባት ነው። (በነገራችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕተብ ማሰርን ያስተማረ አባትም ነው።)
ሁለቱ (አባ ቴዎዶስዮስና ቅዱስ ያዕቆብ) ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ስለ ደከሙ የዘመኑ ምዕመናን በስማቸው "ያዕቆባውያን እና ቴዎዶስዮሳውያን" ተብለው ተጠርተዋል። አባ ቴዎዶስዮስ ግን ሲታሠር ሲፈታ ሲሰደድ ሲመለስ ብዙ ተሰቃየ።
ሕዝቡን ግን በመልካም እረኝነት ጠብቆ ከተኩላ አፍ ታደገ። በዚህች ቀንም ዐርፎ ተቀብሯል። በፓትርያርክነት ያገለገለባቸው ዘመናት ሠላሳ ሁለት ዓመታት ሲሆኑ ከእነዚህ ዓመታት ሃያ ስምንቱ ያለቁት በስደትና በመከራ ነው።
እግዚአብሔር የአባቶቻችን ስደት አስቦ ከነፍስ ስደት ይሰውረን። ከበረከታቸውም ያድለን።
ሰኔ ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ቴዎዶስዮስ ሊቀ ጳጳሳት
፪.ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ
፫.ቅዱስ ባስልዮስ
፬.ቅዱስ ባሊዲስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ። ሐሴትም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና።"
(ማቴ ፭፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን <3
ቅዱሱ የተወለደው በምድረ ግብጽ በባርነት ከነበሩ እስራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ "አውሴ" ይባላል። ዘመኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር። እስራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ ሰማንያ ዓመቱ ኢያሱ ደግሞ አርባ ዓመቱ ነበር።
ሕዝቡ አንገተ ደንዳና ነበርና ለአርባ ቀን የታሠበላቸውን መንገድ አርባ ዓመት እንዲሆን አደረጉት። በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምህሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም።
አውሴን "ኢያሱ" ብሎ ስም የቀየረለት ሙሴ ሲሆን ይሔውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነው። ኢያሱ ማለት "መድኃኒት" ማለት ነው።
ለዚህም ምክንያቶች አሉት። ለጊዜው አማሌቃውያንን ድል ነስቶ ሕዝቡን አድኗል። ምድረ ርስትን አውርሷል።
ለፍጻሜው ግን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ (ጥላ) እንዲሆን ነው።
ቅዱስ ኢያሱ በበርሃ ለአርባ ዘመናት እግዚአብሔርን አምልኮታል። ሊቀ ነቢያትን ታዝዞታል (አገልግሎታል)። እስራኤልንም የጦር አለቃ ሆኖ ከአሕዛብ እጅ አድኗቸዋል።
በዚህም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል። ቅዱስ ሙሴ ደብረ ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን፣ ካህናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ። ይህን ጊዜ ዕድሜው ሰማንያ እየሆነ ነበር።
እግዚአብሔርም ኢያሱን "ከአንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በሕዝቡ ላይ ነቢይና መስፍን (አስተዳዳሪ) እንዲሆን ሾመው። ቅዱሱም ሰላዮችን ልኮ አስገምግሞ፣
ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍሎ፣
ሕዝቡን አሻግሮ፣
የኢያሪኮን ቅጥር ሰባት ጊዜ ዙሮ፣
በኃይለ እግዚአብሔር አፍርሶ፣
የኢያሪኮን ነገሥታት አጥፍቶ ለሕዝቡ ምድረ ርስትን አወረሰ።
የገባዖን ሰዎች "አድነን" ብለው በላኩበት ጊዜ ነገሥተ አሞሬዎንን ይወጋ ዘንድ ኢያሱ ወጣ። እነዚያን ግሩማን ነገሥታት በፈጣሪው ኃይል፣ በጦርና በተአምራት ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ስሙ ከፍ ከፍ አለ። በዚያች ዕለትም ለአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ርስትን ሲያካፍል ፀሐይን በገባዖን ጨረቃን ደግሞ በቆላተ ኤሎም (በኤሎም ሸለቆ) አቆመ።
ሰባት አሕጉራተ ምስካይ (የመማጸኛ ከተሞችን) ለየ። ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝቡን ለአርባ ዓመታት አገለገለ። በመጨረሻም ለሕዝቡ አላቸው።
"እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን። (ኢያ. ፳፬፥፲፭) እናንተስ?" አላቸው። እነርሱም "እኛም እንዳንተ ነን።" አሉት። ለዚህም ምልክት ይሆን ዘንድ ሦስት ገጽ ያላት ሐውልትን በመካከላቸው አቆመ።
ይህችውም የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ሐውልቷ ሦስት ገጽ እንዳላት እመቤታችንም በሦስት ወገን (በነፍስ፣ በሥጋ፣ በልቡና) ድንግል ናት። አንድም በሦስት ወገን (ከኃልዮ፣ ከነቢብ፣ ከገቢር ኃጢአት) ንጽሕት ናት። ለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ
"ሐውልተ ስምዕ ዘኢያሱ" (የኢያሱ የምስክር ሐውልት አንቺ ነሽ።) ሲል ያመሰገናት።
ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን ከግብጽ በወጡ በሰማንያ ዓመት በተወለደ በመቶ ሃያ ዓመቱ (ጥሬው መጽሐፍ ቅዱስ በመቶ አሥር ዓመቱ ይላል።) በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ። እስራኤልም ለሠላሳ ቀናት አለቀሱለት።
በወዳጁ በኢያሱ እጅ የአሕዛብን ቅጥር ያፈረሰ እግዚአብሔር የእኛንም የኃጢአታችንን ግንብ በወዳጆቹ ምልጃ ያፍርስልን። ከቅዱሱ ነቢይም በረከትን ያሳትፈን።
ሰኔ ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን
፪.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት (ቅዳሴ ቤቱ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
"አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ። በእውነተኛም ልብ አምልኩት።
..... እግዚአብሔርን ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ..... የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።"
(ኢያ ፳፬፥፲፬-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅና ገዳማዊ ቅዱስ ሙሴ ጸሊም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ሙሴ ጸሊም (ጥቁሩ ሙሴ) <3
ግብጻውያን ስማቸውን ጠርተው ከማይጠግቧቸው ቅዱሳን መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊው አባ ሙሴ ጸሊም ነው። በእኛ ኢትዮጵያውያን ግን ይቅርና በወርኀዊ በዓሉ (በ፳፬) በዓመታዊ በዓሉ እንኳ ሲከበር ብዙም አይታይም።
ቅዱሱ ሰው በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን ያደገውም እዚሁ ሃገራችን ውስጥ እንደሆነ ይታመናል። ገና በወጣትነቱ ሃገር የሚያሸብር ሽፍታ ነበር። ሙሴ ጸሊም ወደ ግብጽ የሔደበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም መምለክያነ ጣዖት (ፀሐይን ከሚያመልኩ ሰዎች) ጋር ይኖር ስለ ነበር ምናልባት እነርሱ ወስደውት ሊሆን ይችላል።
ቅዱስ ሙሴ በምድረ ግብጽም በኃይለኝነቱ ምክንያት የሚደፍረው አልነበረም። ፀሐይን ያመልካል። እንደ ፈለገ ቀምቶ ይበላል። ያሻውን ሰው ይደበድባል። ነገር ግን በሕሊናው ስለ እውነተኛው አምላክ ይመራመር ነበርና አንድ ቀን ፀሐይን "አምላክ ከሆንሽ አናግሪኝ?" አላት። እርሷ ፍጡር ናትና ዝም አለችው።
ቅዱስ ሙሴ ምንም አስቸጋሪ ሰው ቢሆንም ፈጣሪን መፈለጉን ግን ቀጥሏልና አንድ ቀን ተሳካለት። መልካም ክርስቲያኖችን አግኝቶ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ቢሔድ በዛ ያሉ መነኮሳት ወደ እውነት እንደሚመሩት ነገሩት። እርሱም ሰይፉን እንደታጠቀ ወደ ገዳም ገባ። መነኮሳቱ ፈርተውት ሲሸሹ ታላቁ አባ ኤስድሮስ ግን ተቀብለው አሳረፉት።
"ምን ፈለግህ ልጄ?" አሉት። "እውነተኛውን አምላክ ፊት ለፊት ማየት እፈልጋለሁ።" የሙሴ ጸሊም መልስ ነበር። አባ ኤስድሮስም "የማዝዝህን ሁሉ ካደረግህ ታየዋለህ።" ብለው ወደ መነኮሳት አለቃ ቅዱስ መቃርስ ታላቁ ወሰዱት።
መቃሬም ክርስትናን አስተምረው አጠመቁትና ለአባ ኤስድሮስ መለሱላቸው።
ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር የአባ ሙሴ ጸሊም ሕይወት ፍጹም የተለወጠው። በጻድቁ እጅ ምንኩስናን ተቀብሎ ይጋደል ጀመር። በጠባቧ በር ይገባ ዘንድ ወዷልና ያ በሽፍትነት የሞላ አካሉን በገድል አረገፈው። ከቁመቱ በቀር ከአካሉ አልተረፈለትም። ወገቡን በአጭር ታጥቆ መነኮሳትን አገለገለ። አጋንንት በቀደመ ሕይወቱ በሕልም አንዳንዴም በአካል እየመጡ ይፈትኑት ነበር።
እንዳልቻሉት ሲረዱ ተሰብስበው መጥተው በእሳት አለንጋ ገርፈው አቆሳስለውት ሔዱ። እርሱ ግን ታገሰ። በበርሃ ለሚኖሩ አበው መነኮሳት ሁሉ ብርሃን በሆነ ሕይወቱ ሞገስ ሆነላቸው። ለኃጥአን ደግሞ መጽናኛ ሆነ።
"በተራራ ላይ ያለች ሃገር ልትሠወር አይቻላትምና ስም አጠራሩ በመላው ዓለም ተሰማ። ሁሉም 'ሙሴ ጸሊም' ይል ጀመር።"
በየበርሃው ያሉ አበው ብቻ ሳይሆን ዓለማውያን መኳንንት ሳይቀሩ ሊያዩት ይመኙ ነበር። እርሱ ግን ራሱን "አንተ ጥቁር ባሪያ ስለ ኃጢአትህ አልቅስ።" እያለ ይገስጽ ከውዳሴ ከንቱም ይርቅ ነበር። ከቆይታ በኋላም በመነኮሳት ላይ እረኛ (አበ ምኔት) ሆኖ ተሾመ። እንደሚገባም አገለገለ። የበርካቶችን ሕይወት ጨው በሆነ ሕይወቱና ምክሩ አጣፍጦ ድርሳናትንም ደርሶ እያረጀ ሔደ።
ከቁመቱ መርዘም የጽሕሙ ነጭነትና አወራረዱን ያዩ ሁሉ ሲያዩት ያደንቁት ነበር። በመጨረሻም በ፫፻፸፭ ዓ.ም በርበሮች (አሕዛብ) ገዳመ አስቄጥስን ሲያጠፉ ሌሎች መነኮሳት ሸሹ። እርሱ ግን አልሸሽም ብሎ ከሰባት ደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚህች ቀን ተሰይፎ በሰማዕትነት አልፏል።
ቅዱስ ሙሴ ጸሊምን ለርስቱ ያበቃ ጌታ ለእኛም ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሃን አይንሳን። ከበረከቱም ፈጣሪው ያድለን።
ሰኔ ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮጵያዊ)
፪.ሰባቱ ቅዱሳን መነኮሳት (ደቀ መዛሙርቱ)
፫.አባ ኤስድሮስ ታላቁ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤጲስቆጶስ)
፫.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮.ሃያ አራቱ ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
፯.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል። ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ "የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ።" ይላቸዋል። እላችኋለሁ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።"
(ሉቃ ፲፭፥፬-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ነቢይ፣ ጠቢብና የእስራኤል ንጉሥ ቅዱስ ሰሎሞን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል <3
መፍቀሬ ጥበብ፣
ጠቢበ ጠቢባን፣
ንጉሠ እስራኤል፣
ነቢየ ጽድቅ፣
መስተሣልም (ሰላማዊ) እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ሰሎሞን የታላቁ ነቢይና ንጉሥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እና የቅድስት ቤርሳቤህ (ቤትስባ) ልጅ ነው። ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት የተወለደው ቅዱስ ሰሎሞን እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ ድረስ በቤተ መንግሥት ከአባቱ ጋር አድጓል።
ቅዱስ ዳዊት ሰባ ዘመን በሞላው ጊዜ የአካሉን መድከም አይቶ አዶንያስ በጉልበት እነግሣለሁ ቢልም አልተሳካለትም። እግዚአብሔር ሰሎሞንን መርጧልና ገና በአሥራ ሁለት ዓመቱ ነገሠ። ልበ አምላክ አባቱ ዳዊት ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት መከረው። "ልጄ ሆይ! ልብህን ስጠኝ። ፈጣሪህንም አምልክ።" አለው።
ቅዱስ ሰሎሞን እንደ ነገሠ በገባዖን ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረበ። ጌታም ተገልጾ "ምን ትፈልጋለህ?" አለው። ሰሎሞንም ልክ እንደ አባቱ ማስተዋልን ልቡናን ለመነ። በዚህም ጌታ ደስ ስለተሰኘ "አልቦ እምቅድሜከ ወአልቦ እምድኅሬከ - ከአንተም በፊት ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ ጠቢብና ባለጠጋ ሰው የለም፤ አይኖርም።" ብሎት ተሠወረ። ቅዱስ ሰሎሞን ለአርባ ዓመታት በእስራኤል ላይ ነገሠ።
ግሩም በሆነ ፍትሑ በልዩ ጥበቡ ዓለም ተገዛለት። እግዚአብሔር የመረጣት የእኛዋ ንግሥተ ሳባ /አዜብ/ ማክዳም ትፈትነው ዘንድ ሒዳ ምኒልክን (እብነ መለክን) ጸነሰች። በኋላም ታቦተ ጽዮንና ሥርዓተ ኦሪት መጣልን። ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን ድንግል ማርያም ከእነርሱ ዘር እንደምትወለድ ነግሮት ነበርና ያበጀሁ መስሎት ሴቶችን አብዝቶ ነበር።
ነገር ግን፦
አንደኛ ሰው (ሥጋ ለባሽ) ነውና።
ሁለተኛ ደግሞ ከብዙ ሴቶች መካከል ከአንዷ እመ ብርሃን ትገኛለች መስሎት ነበር። ነገሩ መንገድ ስቶበት ከአሕዛብ (ከፈርዖን ልጅ) ጋር በመወዳጀቱ ለጣዖት አሰገደችው። እግዚአብሔር እጅግ አዘነ።
በራእይ ተገልጦ "ስለ ወዳጄ ስለ ዳዊት ስል በአንተ ላይ ክፉን አላደርግም።" አለው። ታላቁ ነቢይ ሰሎሞን ይህንን ሲሰማ ወደ ልቡ ተመለሰ። ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ በፍጹም ልቡ አለቀሰ። ንስሐ ገባ። መፍቀሬ ንስሐ ጌታችንም ንስሐውን ተቀበለው።
የይቅርታው መገለጫም ተወዳዳሪ የሌላቸውን አምስት መጻሕፍት ገለጠለት፤ ተናገራቸው። ጻፋቸው።
እሊሕም፦
፩.መጽሐፈ ጥበብ
፪.መጽሐፈ ተግሣጽ
፫.መጽሐፈ መክብብ
፬.መጽሐፈ ምሳሌ
፭.መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው።
ቅዱስ ሰሎሞን ልዩ የሆነውን ቤተ መቅደስ በመስራቱም ይደነቃል። ደጉ ንጉሥ፣ ጠቢብና ነቢይ ሰሎሞን በዚህች ዕለት በሃምሳ ሁለት ዓመቱ ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሔዷል።
<3 አባ ኖብ <3
ዳግመኛ በዚህች ቀን ታላቁ ሰማዕት አባ ኖብ ዐርፏል። በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ቢኖሩም ዋናው ይኼው ቅዱስ ነው።
አባ ኖብ እንደ ገዳማውያን በበርሃ የተጋደለ፣ እንደ ሊቃውንት መጻሕፍትን ያመሰጠረ፣ በተለይ ደግሞ በዘመነ ሰማዕታት ጭንቅ ጭንቅ መከራዎችን የተቀበለ አባት ነው። ስለ ገድሉ ብዛት "ኃያል ሰማዕት" አንገቱን ስላልተቆረጠም "ሰማዕት ዘእንበለ ደም" ይባላል። ዘመነ ሰማዕታትን ካለፉ ሰባ ሁለቱ ከዋክብትም አንዱ ነው።
ከመፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን ከኃያሉ ሰማዕት አባ ኖብ በረከትን አምላካችን ይክፈለን።
ሰኔ ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እስራኤል)
፪.ቅዱስ አባ ኖብ (ሰማዕት ወጻድቅ)
፫.ቅዱሳን መርቆሬዎስ፣ ፊልጶስና ቶማስ (ሰማዕታት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፬.አባ ሳሙኤል
፭.አባ ስምዖን
፮.አባ ገብርኤል
፯.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
"የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ። ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ..... አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።
ሰባኪው 'ከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው።' ይላል።"
(መክ ፲፪፥፩-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
"በሠላስ አእባን ገጸ ሥላሴሁ ለአምሮ
ሐኒጸ ቤትኪ ድንግል ድኅረ ፈጸመ ሣርሮ
አመ ወረደ ለበዓል ምስሌኪ በአማኅብሮ
እንዘ ይብላ ቃለ ለዘምሮ
ልዑል ቀደሰ ማኅደሮ
ደናግል ለጽጌኪ ዘበጣ ከበሮ።"
(ድንግል በአካል ሦስት መሆኑን ለመግለጽ በሦስት ድንጋዮች ቤትሽን መሥራት ከፈጸመ በኋላ፤ ከአንቺ ጋር ለበዓል በተገለጸ ጊዜ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ እያሉ ልጅሽን ለማመስገን ደናግል በከበሮ ምስጋናን አቀረቡ።)
(አባ ጽጌ ድንግልወ አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ)
"ሰላም ለቤተ ክርስቲያን ቅድስት ማኅደረ ስብሐት ምዕዋደ መላእክት እመ ኲሉ ሕዝብ።"
(የሕዝብ ሁሉ እናት የመላእክት መዘዋወሪያ (ቦታ) የምስጋና ማደሪያ ለሆነችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ይገባል።)
(አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)
እንኳን ለሐዲስ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ <3
ሰማዕቱ የተወለደው በምድረ ግብጽ አሕዛብ (ተንባላት) በሰለጠኑበት የመጀመሪያው ዘመን ነበር። በተለይ ተንባላቱ ግብጽና ሶርያን ከያዙ በኋላ ባልተጠበቀ ፍጥነት በኃይልም በሰውም ተደራጅተው ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ (ልብ በሉልኝ ሊቀ ሰማዕታት አይደለም።) የተወለደው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር።
እናቱ የተመሠከረላት ክርስቲያን ብትሆንም እንዳለመታደል አባቱ ተንባላታዊ (አሕዛብ) ነበር። ስሙንም "መዛሕዝም" ይሉታል። ሕፃኑ እንደተወለደ ያወጡለት ስም አሕዛባዊ ከመሆኑ ባለፈ በሰዓቱ መጠመቅ አልቻለም። የወቅቱ ሕግ ከወላጆቹ አንዱ አሕዛባዊ ከሆነና አጠምቃለሁ ቢባል የሚከተለው ሰይፍ ነበር። በዚህ ምክንያት ሳይጠመቅ ሰባት ዓመት ሞላው።
እናቱ ግን ሕፃን ቢሆንም ፍቅረ ክርስትናን ታስተምረው ነበር። ባይጠመቅም ጠበሉን፣ እመቱን ትቀባው ነበር። ደብቃ ቅዳሴ ታሰማውም ነበር። አንድ ቀን ግን ሕፃናት ሲቆርቡ አይቶ "ካልቆረብኩ" ብሎ አለቀሰ። ምን ታድርገው? ወደ ውጪ አውጥታ ከአውሎግያ (የሰንበት በረከት) አበላችው። "ጌታዬ! ልጄን እርዳው።" አለች።
ልክ በአፉ ሲቀምሳት መዓዛ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና ፍጹም ተደሰተ። ትንሽ ከፍ ሲል ለምን እንደማይጠመቅና እንደማይቆርብ እናቱን ጠየቃት። "ልጄ ሆይ! ይገድሉሃል።" አለችው።
ከዚህች ቀን ጀምሮ የሚጠመቅበትን ዘዴ ይፈልግ ጀመር።
አስቀድሞ ትምሕርተ ክርስትናን ተማረ። ለአካለ መጠን ሲደርስ አፈላልጐ ጠንካራ ክርስቲያን የሆነች ሴት አገባ። ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ሚስቱን ስለ መጠመቅ አማከራት። "ሌላ ሃገር ሒደህ ተጠመቅ።" አለችው።
ከግብጽ ተነስቶ ሶርያ ገባ። አባቶችንም አፈላልጎ ተጠመቀ። ቀጥሎም መንገዱን ወደ ልዳ አደረገ።
ወደ ደብሩ ተጠግቶ አባቶችን "ስም አውጡልኝ።" ቢላቸው መንፈስ ቅዱስ አናግሯቸው "ጊዮርጊስ" አሉት።እርሱም ደስ እያለው ባጭር ታጥቆ የልዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገለግለው ገባ። ትንሽ ቆይቶ ሁከት መንፈሳዊ ተሰማው። ማለትም ስለ ሃይማኖቱ ደሙን ማፍሰስ ፈለገና ወደ ግብጽ ተመለሰ።
በዚያ ያሉ አሕዛብ በክርስትና ስም፣ ልብስና ሞገስ ሲመለከቱት ተበሳጩ፤ ዕለቱኑ አሠሩት። ሌሊት እናቱና ሚስቱ መጥተው አሉት፦
"አደራ! ፍቅረ ዓለም እንዳያታልልህ። ሰማዕት ብትሆን ላንተም ክብር ለእኛም ሞገስ ነው።" ብለውም አጽናኑት። (እንዲህ ያሉ እናትና ሚስት ማግኘትም ታላቅ እድል ነው!)
ሐዲስ ጊዮርጊስም ጸና። ከዚያች ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ደበደቡት። አካሉን ቆራረጡት። ደሙንም መሬት ላይ አንጠፈጠፉት። በየመንገዱ እየጎተቱ ተሳለቁበት። እርሱ ግን ክርስቶስን ወዷልና ሁሉን ታገሰ። ሌሊት በሆነ ጊዜም ጌታችን ተገልጦ "ከሰማዕታት ተቆጠርህ።" አለው።
በማግስቱ በአደባባይ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት። ክፋታቸው የጸና ነውና ሥጋውን በእሳት አቃጠሉት። ወደ ባሕርም ጣሉት። እናቱ ከባሕር ስታወጣው ግን ምንም አላገኘውም ነበር። በዚህች ቀንም እናቱና ሚስቱ በክብር ቀብረውታል።
ቸሩ አምላክ ከሰማዕቱ ጽናትን፣ ትእግስትን፣ ጸጋ በረከትን ይክፈለን።
ሰኔ ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ ሰማዕት
፪.አባ ብሶይ አኖብ ሰማዕት (በአንበሳ ጀርባ ላይ የተቀመጠ አባት)
፫.ቅዱሳን አምስቱ ጭፍሮች (በብዙ ስቃይ ሰማዕት የሆኑ ባልንጀሮች)
፬.አባቶቻችን የደብረ ቋዐት ጻድቃን
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፬.አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም
"ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ። በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?
.....እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን። ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።"
(፩ቆሮ ፲፥፲፬-፲፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃን አበው አባ ገሪማ፣ አባ ለትጹን እና አባ ጰላሞን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ <3
አቡነ ገሪማ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሮም ውስጥ ነው። ወላጆቻቸው መስፍንያኖስ እና ሰፍንግያ እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት ነበሩ። ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ።
እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው። ስሙን ይስሐቅ ብለው አሳደጉት። ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ። ለሰባት ዓመታት ሕዝቡን በፍትሕ እያስተዳደረ፣ መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል።
አንድ ቀን ግን ከግብጽ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው። ላኪው አባ ጰንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ ንግሥና ምን ያደርግልሃል? ይልቁኑስ በሰማይ ለዘላለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና!" የሚል ነበር።
ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ። ድንገት ግን ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብጽ አባ ጰንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው።
እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው። ሰውነታቸውን በገድል ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር።
አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው አባ ጰንጠሌዎን አዘኑ። ልምከረው ብለው "ልጄ ይስሐቅ የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ።" አሉ። አባ ይስሐቅ ግን "ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል።" ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (ሁለት መቶ ሜትር) ተጠራርጎ ሸሸ።
ይህንን የተመለከቱት አባ ጰንጠሌዎን "ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)።" አሏቸው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም "አቡነ ገሪማ" ተብለው ቀሩ።
አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም ግሩም ነህ።" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል።
ጻድቁ ወንጌልን ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል።
፩.ስንዴ ጧት ዘርተውት በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር። "በጽባሕ ይዘርዕ ወበሠርክ የአርር" እንዲል።
፪.ጧት የተከሉት ወይን በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር።
፫.አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጠበል ሆኖ ዛሬም አለ።
፬.ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች።
፭.አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን አቁመዋታል።
ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። "ስምህን የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ እስከ አሥራ ሁለት ትውልድ እምርልሃለሁ። አንተ ግን ሞትን አትቀምስም።" ብሏቸው ተሰወረ። ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ ብሔረ ሕያዋን አድርሰዋቸዋል።
<3 አባ ለትጹን የዋሕ <3
ስመ ጥሩ ጻድቅ አባ ለትጹን በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግብጽ የተወለዱ፣
በፍጹም ተግሣጽ ያደጉ፣
ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን በሕገ ወንጌል የመሩ፣
አንድ ቀን በሰሟት የወንጌል ቃል የመነኑ፣
ገዳም ገብተው በትሕትና ለዘመናት ያገለገሉ፣
በመጨረሻም ወደ ትልቅ ተራራ ወጥተው ተጋድሏቸውን የፈጸሙ ታላቅ አባት ናቸው።
ከየዋሕነታቸው የተነሳ ኃጢአተኛ ሰው ሲያገኙ ራሳቸው ንስሐ ይገቡ ነበር። አንዴ ግን እናቱን አሥር ጊዜ በዝሙት ያረከሰ ስትጸንስም መርዝ አጠጥቶ ጽንሱን በማኅጸኗ የገደለና በሥጋ ወደሙ ላይ የተዘባበተ ሰው ሊሞት ሲል ደረሱ።
አጋንንት ሲዖል ታች ሲጥሉትም ተመለከቱ። ኃጢአቱ ጭንቅ ቢሆንም የእርሱን ንስሐ ሊቀበሉ ጀመሩ። ከንስሐቸው ጽናት የተነሳ ሞቱ። ጌታችን ከሞት አስነስቶ "አትለምነኝ፤ አልምረውም።" አላቸው።
ጻድቁ ተስፋ አልቆረጡምና ቀጠሉ። ለሁለተኛ ጊዜ ሞቱ፤ አሁንም ቀጠሉ። ሦስተኛ፣ አራተኛ፣ አምስተኛ ጊዜም ሞቱ። በስድስተኛው ግን መፍትሔ መጣ። ጌታችን አእላፍ መላእክትን አስከትሎ ያችንም ኃጥእ ነፍስ ይዞ መጣ። "ፍርዴ አይታጠፍምና ወደ ገነት አላስገባትም። ስለ አንተ ጽድቅና የዋሕነት ደግሞ ሲዖል አልጥላትም። ስለዚህም እንዳልተፈጠረች ትሁን።" ብሎ እፍ አለባት። ፈጥና ወደ ትቢያነት ተቀየረች።
ጻድቁም የፈጣሪያቸውን ቸርነት አድንቀው ሰገዱ። ከብዙ ዘመናት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐረፉ።
<3 አባ ጰላሞን ፈላሲ <3
ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ ገዳማውያን አንዱ አባ ጰላሞን የአባ ለትጹን ወዳጅ ነበር። ይህ ቅዱስ ከአጋንንት ጋር በገጠመው ጦርነት ምክንያት ለየት ይላል። ከስልሳ ዓመታት በላይ እንኳን ሳቅና ደስታ ቀና ብሎም ሰው አላየም።
በእነዚሁ ዘመናት ሁሉ ቅንድቡ እስኪላጥ አልቅሷል። በዓለም ያሉ አጋንንት ሁሉ ተሰብስበው አሰቃይተውታል። እርሱ ግን በእግዚአብሔር ቸርነት በወዳጁ በአባ ለትጹን ጸሎትና በትጋት አሸንፏቸው ዛሬ ዐርፏል።
ቸሩ አምላካችን ከታላላቁ ቅዱሳን ጸጋ በረከት ይክፈለን። በምልጃቸውም ይቅር ይበለን።
ሰኔ ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ብጹዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
፪.አባ ለትጹን ዐቢይ ወየዋሕ
፫.አባ ጰላሞን ፈላሲ
፬.ቅድስት አርሴማ ጻድቅት
፭.ሰማዕታት እለ አኮራን
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
፫.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆጵሮስ)
"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና። ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና። ለዘለላምም ይጠብቃቸዋል።.....
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ ሚናስ ዓመታዊ የቅዳሴ ቤት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ሚናስ ምዕመን ሰማዕት <3
ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) በምድረ ግብጽ ተወዳጅ ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው ነው። ልክ በሃገራችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዩ ቦታ እንዳለው ሁሉ ግብጻውያን ማር ሚናስን ጠርተው አይጠግቡትም።
ምክንያቱም ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ በመሆኑና ዛሬም ድረስ ለጆሮና ለዓይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ስለሚሠራ ነው። በተለይ ለታመመ፣ ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ ደራሽ ባለ በጐ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ ነው።
ግብጽ ውስጥ ቅዱሱን የማያውቅ ሰው ካገኛችሁ እርሱ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም ማለት ነው ሲባልም ሰምተናል። በነገራችን ላይ ለቅዱሳን ተገቢውን ክብር በመስጠት፣ ታሪካቸውን በመጻፍ፣ በማጥናት፣ በመጽሔት፣ በፊልምና በመሳሰሉት ለሕዝብ በማስተዋወቅ ግብጻውያኑ ከእኛ ብዙ ርቀት ሔደዋል። ዛሬ እንኳ የምንጠቀምበትን ስንክሳር ሰማንያ ከመቶ እጁን ያዘጋጁት እነርሱ ናቸው።
አባቶቻችንና እናቶቻችን ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ግን አብዛኞቹ ተረስተው ቀርተዋል። መጽሐፈ ገድላቸውንም ብል በልቶታል። ዛሬም የቤት ሥራው የእኛ ብቻ ነው።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ ሚናስ (ትርጉሙ ታማኝና ቡሩክ ማለት ነው።)
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ የደጋግ ክርስቲያኖች ልጅ፣
በልጅነቱ የቅድስና ሕይወትን ያጣጣመ፣
በዘመኑ ሰው እጅግ ተወዳጅ የነበረ፣
ሃብትን፣ ክብርን፣ ሥልጣንን ንቆ በጾምና በጸሎት የተወሰነ፣
በመጨረሻም በክርስቶስ ስላመነ አላውያን የገደሉት ሰማዕት ነው።
እርሱ ሰማዕት ከሆነ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ምዕመናን ክቡር አካሉን ፈልገው ያጡታል። የሚገለጥበት ጊዜ ሲደርስ ግን እርሱ የተቀበረበት ምድረ በዳ የበጐችና የእረኞች መዋያ ነበርና ተአምራትን አደረገ። አንድ እረኛ በጐቹ ድውያን ሆኑበት። በዚያ ሰሞን ከቅዱሱ መቃብር ላይ ጠበል ፈልቆ ነበርና እረኛው ተርታ ውኃ ነው ብሎ በጎቹን ሲያጠጣቸው አንዱ ድውይ በግ ወደ ጠበሉ በመዘፈቁ ዳነ።
በዚህ የተገረመው እረኛ ሁሉንም የታመሙ በጐቹን አምጥቶ ነከራቸው። እነርሱም ተፈወሱ። ይህ ዜና በምድረ ግብጽ ሲሰማ ድውያን ሁሉ እየመጡ ይፈወሱ ገቡ። ግን እነርሱም ሆነ እረኛው ምክንያቱን ማወቅ አልቻሉም።
ነገሩ በሮም ንጉሥ ዘንድ ሲሰማ ሴት ልጁን ከሠራዊቱ ጋር ላካት። ምክንያቱም እርሷ ከብዙ ዘመን ጀምራ መጻጉዕ ነበረችና ፈውስን አጥታ ነበር። መጥታ ተጠመቀች። ፈጥናም ተፈወሰች። እርሷ ግን እንደ ሌሎች ያዳናትን ማንነት ሳታውቅ መሔድ አልፈለገችምና ሱባዔ ገባች።
ቅዱስ ሚናስ በሌሊት ራእይ መጥቶ ሥጋው እንዳለ ነገራት። እርሷም መሬቱን አስቆፍራ የቅዱሱን አካል በክብር አስወጣች። ከዚያም በንጉሡ ትዕዛዝ ምድረ በዳው ከተማ እንዲሆን ተቀየረ። ስሙም "መርዩጥ" ተባለ። ጠበሉ የነበረበት ቦታም ላይ የማር ሚናስ ቤተ ክርስቲያን ታንጾበት በዚህች ዕለት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል።
አምላካችን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከትን ይክፈለን።
ሰኔ ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፫.ቅድስት እንባ መሪና
፬.ቅድስት ክርስጢና
"ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። ብዘገይ ግን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ። ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። እግዚአብሔርንም የመምሠል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው።"
(፩ጢሞ ፫፥፲፬-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል እና ለጻድቁ አባ ዮሐንስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት <3
ቅዱስ ገብርኤል፦
በራማ ከሚኖሩ ሊቃናት አንዱ፣
አርባብ በሚባሉ አሥር ነገዶች ላይ አለቅነትን የተሾመ፣
የስሙ ትርጓሜ "እግዚእ ወገብር" (ጌታና አገልጋይ) አንድም "አምላክ ወሰብእ" (የአምላክ ሰው መሆን) ማለት የሆነ፣
በመጀመሪያዋ የፍጥረት ቀን ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ያረጋጋ፣
ብርሃናውያን መላእክትን የሚመራ፣
በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት አብሣሪነቱ በስፋት የተነገረለት፣
በተለይ ደግሞ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው የመሆን ዜና ይሸከም ዘንድ ያደለው፣
ከድንግል ማርያም ጎን በፍጹም የማይርቅና በፈጣን ተራዳኢነቱ ብዙ ቅዱሳንን ያገለገለ ታላቅ ቀናዒ መልአክ ነው።
በዚህች ዕለት እግዚአብሔር ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ባቢሎን ልኮታል። ሊቀ መላእክት ነቢዩ ዳንኤልን ከአናብስቱ ጥርስ እንዳዳነው መጽሐፍ ነግሮናል።
ይልቁኑ ታላቁ ነቢይ ዳንኤል የተማረኩ ወገኖቹን መመለስ እያሰበ በሃዘን ሲጸልይ በዚህች ቀን ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ዳስሶታል፤ ባርኮታል፤ አጽናንቶታል። ለዳንኤል በዋነኛነትም ሦስት ምሥጢራትን ገልጾለታል።
፩.የቤተ እስራኤልን ከሰባ ዘመን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ
፪.የክርስቶስን ሰው መሆንና መሞት
፫.የሐሳዌ መሲሕን በመጨረሻ ዘመን መምጣት ነግሮታል። ስለዚህም እኛ ቅዱስ ገብርኤልን እንድናከብረው በጸሎትም እንድንጠራው አባቶቻችን አዝዘውናል።
<3 አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም <3
ጻድቁ ሃገራቸው መካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ሲሆን የታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ባልንጀራ ናቸው። ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በክርስትና አድገው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው ወደ ገዳም መንነዋል።
ከታላቁ ኮከበ ገዳም አባ ኢላርዮን ሥርዓተ መነኮሳትን አጥንተው አባ ኤስድሮስን በረድዕነት አገልግለዋል።
ከብዙ ዓመታት ትሕርምትና ገዳማዊ ሕይወት በኋላ የቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ጳጳስ ሆነው ተሹመዋል። በጵጵስናቸው ዘመን አንድ ከባድ ስሕተት ሠርተው ነበር።
እርሱም ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ከምእመናን የተሠበሠበውን ገንዘብ ለግል ጉዳያቸው አውለው ልብሳቸውና ቤታቸው ወርቅ በወርቅ ሆኖ ነበር። ፈጣሪ ግን ይህንን ብክነት ከእርሳቸው ያርቅ ዘንድ ቅዱስ ኤጲፋንዮስን ላከው።
እርሱም በምክንያት ከቆጵሮስ ኢየሩሳሌም ገባ። ጓደኛ ናቸውና አሳምኖ የወርቅ ንብረቶቹን ሁሉ ወሰደ። ለነዳያንም ሰጣቸው። አባ ዮሐንስ ሊቁን "እቃዬን ካልመለስክ" ብለው ቢይዙት ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ጸልዮ ዓይናቸው እንዲታወር አደረገ። አንዳንዴ የታወረ ልብ የሚገለጠው እንዲህ ነውና።
በደቂቃዎች ልዩነት ዓይነ ስውር የሆኑት አባ ዮሐንስ አለቀሱ። ሊቁንም "ራራልኝ፤ አማልደኝ?" አሉት። እርሱም ጸልዮ አንድ ዓይናቸውን ብቻ አበራላቸው። "ለምን?" አሉት። "ተግሣጽ ነው።" አላቸው።
ከዚያች ቀን በኋላ አባ ዮሐንስ ወደ ልቡናቸው ተመለሱ። ቤታቸውን ገዳም አደረጉት። በሚደነቅ ቅድስና፣ ፍቅርና ሐዋርያዊ አገልግሎት ምዕመናንን አገልግለው በዚህች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፈዋል።
የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ረድኤት የአባ ዮሐንስ በረከት አይለየን።
ሰኔ ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት (ወደ ዳንኤል የወረደበት)
፪.አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም
፫.አባታችን ቃይናን (ከአዳም አራተኛ ትውልድ)
፬.አባ ማትያን ጻድቅ
ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬.ቅዱስ አስከናፍር
፭.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ
".....በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ። በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ። አስተማረኝም ተናገረኝም። እንዲህም አለ፦ "ዳንኤል ሆይ! ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።"
(ዳን ፱፥፳-፳፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ማር ገላውዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት <3
ቅዱስ ገላውዴዎስ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በድሮው የሮም ግዛት በአንጾኪያ (አሁን ሶርያ ውስጥ) ነው። አባቱ አብጥልዎስ የሮም ቄሣር የኑማርያኖስ ወንድም ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ያደገው በቤተ መንግሥት ውስጥ ነው።
ወቅቱ መልካምም ክፉም ነገሮች ነበሩት። መልካሙ ነገር በቤተ መንግሥት አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ልዑላኑ አብዛኞቹ በፍቅረ ክርስቶስ የታሠሩ ነበሩ።
ከእነዚህ መካካከል "ቅዱስ ፋሲለደስ፣
ቅዱሳኑ፦ ፊቅጦር፣ ቴዎድሮስ፣ አባዲር፣ አውሳብዮስ፣ ዮስጦስ፣ አቦሊ፣ እስጢፋኖስ....." ነበሩ።
ቅዱሳቱ "ማርታ፣ ታውክልያ፣ ኢራኢ፣ ሶፍያ....." ነበሩ።
አስቸጋሪው ነገር ደግሞ ነጋ መሸ ኑሯቸው ጦርነት ነበር። የዘመኑ የፋርስና የቁዝ መሪዎች ጦረኞች ነበሩና ዕለት ዕለት ፍልሚያ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ገላውዴዎስ የተመሠከረለት አርበኛና የተባረከ ንጹሕ ክርስቲያን ሆኖ አድጓል። ከልጅነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናቱ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ጨውነት ታሽቷል። እርሱ የነገሥታቱ ቤተሰብ ነው። ማዕዱ በየዓይነቱ ሞልቶ ካልመሸ እህል አይቀምስም።
ጸሎቱ ስሙር፣
ስግደቱ ከምድር፣
አኗኗሩ በፍቅር ሆነ። በዚያውም ላይ በድንግልናው የጸና ኃያል ነበር።
በጊዜው የቅዱስ ገላውዴዎስን ያህል መልኩ ያማረ (ደመ ግቡ) በአካባቢው አልነበረም። ይህ ግን ሊያታልለው አልቻለም። ሁሉ በእጁ ቢሆንም ለእርሱ ግን ብቸኛ ምርጫው ሃይማኖተ ክርስቶስ ነበር።
ቅዱስ ገላውዴዎስ ለጦርነት ወጥቶ ሲመለስ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ሃይማኖቱን ክዶ ሕዝቡን ለጣዖት ሲያሰግድ ክርስቲያኖችን ሲገድል ደረሰ።
ቅዱሱ ኃያል የጦር ሰው ነውና ንጉሡን መግደል ሲችል ተወው። በዚያ ሰሞንም ለገላውዴዎስ ሁለት ምርጫዎች ቀረቡለት።
፩.ክርስቶስን ክዶ የንጉሡ ተከታይ መሆን፣
፪.በክርስትናው ደሙን ማፍሰስ።
የቅዱሳኑ ምርጫቸው የታወቀ ነውና ታስሮ ወደ ግብጽ ተጋዘ። በዚያ ከመኮንኑ ጋር ስለ ሃይማኖት ተከራክረው መኮንኑ ስለተበሳጨ ቅዱሱን በረዥም ጦር ጐኑን ወጋው። ዘለፍ ብሎ ነፍሱን ሰጠ። ሕዝበ ክርስቲያኑ በድብቅ መጥተው የቅዱሱን ሥጋ ሽቱ ቀብተው ከዝማሬ ጋር ገነዙት። የጓደኛው እናት ቅድስት ሶፍያ መጥታ ወደ ሶርያ ወስዳዋለች።
ተወዳጅ፣ ኃያል፣ ቡሩክና መልካም ሰው ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት በሆነባት በዚህች ዕለት በመላው ኦርቶዶክሳውያን ይከበራል።
አምላካችን የቅዱሱን መንኖ ጥሪት፣ ትዕግስት፣ ጸጋና በረከት ያሳድርብን። አሜን።
ሰኔ ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት (ሕይወቱ መላእክትን የመሰለ)
፪.አንድ ሺህ ሰማንያ ስምንት ሰማዕታት (የቅዱስ ገላውዴዎስ ማኅበር)
፫.አባ ክርዳኑ ሊቀ ጳጳሳት
፬.እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ክብራ ኢትዮጵያዊት (የአቡነ በጸሎተ ሚካኤል እኅት)
፭.የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዳሴ ቤቱ (ግብጽ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፫.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
፬.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
"የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ። ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ..... አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።
ሰባኪው "ከንቱ፣ ከንቱ፣ ሁሉ ከንቱ ነው።" ይላል።"
(መክ ፲፪፥፩-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሳሙኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል <3
እስራኤል ከግብጽ ባርነት ወጥተው ከነዓንን ከወረሱበት ዘመን ጀምረው መሳፍንትና ካህናት ያስተዳድሯቸው ነበር። በወቅቱ ታዲያ ክህነት ከምስፍና ተስማምቶለት ኤሊ የተባለ ሊቀ ካህናትና ልጆቹ (አፍኒና ፊንሐስ) ያስተዳድሩ ጀመር።
በዘመኑ ደግሞ ማኅጸኗ ተዘግቶባት ዘወትር የምታለቅስ ሐና የሚሏት ደግ ሴት ነበረች። እግዚአብሔር የእርሷን ጸሎትና የሊቀ ካህናቱን ምርቃት ሰምቷልና ቅዱስ ልጅን ሰጣት። "ሳሙኤል" አለችው። "ልመናዬን አምላክ ሰማኝ።" ማለት ነውና።
ሐና ስዕለቷን ትፈጽም ዘንድ ሳሙኤልን በሦስት ዓመቱ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጠችው። በዚያም ስብሐተ እግዚአብሔርን እየሰማ፣ ማዕጠንቱን እያሸተተ፣ ከደብተራ ኦሪቱ ሳይለይ በሞገስ አደገ። የኤሊ ልጆች (አፍኒና ፊንሐስ) ግን በበደል ላይ በደልን አበዙ።
ወቅቱ የአሁኑን ዘመን ይመስል ነበር። ሁሉም ሰው ክፋተኛ የሆነበት በመሆኑ እግዚአብሔር ርቆ ስለ ነበር ትንቢትና ራእይ ብርቅ ነበር። አምላክ ተቆጥቷልና ሳሙኤልን በሌሊት ሦስት ጊዜ ጠራው። ነቢዩም ታጥቆ የፈጣሪውን ቃል ሰማ። በዚህም የተነሳ ታቦተ ጽዮን ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ ተማረከች። ከሠላሳ አራት ሺ በላይ ሕዝብ በኢሎፍላውያን አለቀ። አፍኒና ፊንሐስም ተገደሉ፤ ኤሊም ወድቆ ሞተ።
ከዚህች ቀን በኋላ ቅዱስ ሳሙኤል በእስራኤል ላይ ነቢይና መስፍን ሆኖ ተሾመ። በዘመኑ ሁሉ እንደሚገባው እየኖረ የእግዚአብሔርን ለእስራኤል የእስራኤልን ለእግዚአብሔር ሲያደርስ ኑሯል። ሕዝቡ ንጉሥ በፈለጉ ጊዜ ሳዖልን ቀብቶ አነገሠላቸው። እርሱ (ሳዖል) እንደ ሕጉ አልሔደምና ፈጣሪ ናቀው።
ሳሙኤል ግን ደግ አባት ነውና ክፋተኛውን (ሳዖልን) ከጌታው ጋር ያስታርቅ ዘንድ ብዙ ደከመ፤ አለቀሰም። እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ "አትዘን! እንደ ልቤ የሆነ ፈቃዴን የሚፈጽም ዳዊትን አግኝቸዋለሁና እርሱን በእስራኤል ላይ አንግሠው።" አለው። ቅዱስ ሳሙኤልም ወደ ቤተ ልሔም ሔዶ ከእሴይ ልጆችም መርጦ ልበ አምላክ ዳዊትን ቀባው፤ አነገሠውም።
ቅዱስ ሳሙኤል በተረፈው ዘመኑ ለፈጣሪው እየተገዛ ኑሯል። ነቢዩ ዘወትር ከእጁ የሽቱ ሙዳይና የቅብዐት እቃ (ቀንድ) አይለይም ነበረ። እነዚህም የድንግል ማርያም ምሳሌዎች ናቸውና አባ ሕርያቆስ፦
"ሙዳየ ዕፍረት ወቀርነ ቅብዕ ዘሳሙኤል" ብሎ አመስግኗታል።
ነቢዩም በወገኖቹ መካከል በዚህች ቀን ዐርፏል። እስራኤልም አልቅሰውለታል።
<3 ቅዱስ ሉክያኖስ <3
ዳግመኛ በዚህ ቀን ቅዱስ ሉክያኖስ ይታሠባል።
በቀደመ ሕይወቱ ጣዖት አምላኪና አጣኝ የነበረው ቅዱሱ ማንም ሳያስተምረው ክርስቲያኖቹን በመመልከት ብቻ አምኗል። የወቅቱ ክርስቲያኖች አኗኗራቸው፣ ትጋታቸው፣ ጽናታቸውና ፍቅራቸው እንዲሁ ይስብ ነበር።
ከእነርሱ እምነት መውጣቱን የተመለከቱ ኢ-አማንያን አታልለው ሊመልሱት ሞከሩ። እንቢ ቢላቸው በድንጋይ ጥርሱን አረገፉት። ደሙን አፈሰሱ። አሁንም በሃይማኖተ ክርስቶስ በመጽናቱ በዚህች ቀን ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በመስቀል ላይ ሰቅለው ገድለውታል።
የቅዱሳኑን በረከት አምላካቸው ያድለን።
ሰኔ ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሳሙኤል ነቢይ
፪.ቅዱስ ሉክያኖስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ዮሐንስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
፫.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
፬.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
፮.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)
"እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ። ጽድቅንም አደረጉ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፪-፴፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ <3
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በደራሲነታቸው፣ በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው።
ሊቁ የተወለደው መጋቢት ፳፯ ቀን በ፬፻፴፫ ዓ.ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው። ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር። ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር።
አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት ገና በሦስት ዓመቱ እናቱ አቅፋ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችው። ምዕመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ሕፃኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ። ሊቀ ጳጳሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው። የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምሥጢር ተገለጸለትና "አንሰ እፈርሕ ሠለስተ ግብራተ - እኔስ ሦስት ነገሮች ያስፈሩኛል።" ሲል አሰምቶ ተናገረ።
ጳጳሱና ሕዝቡ ወደ ሕፃኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት።
እርሱም፦
፩.ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ
፪.ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ
፫.ከፈጣሪዬ የፍርድ ቃል ሲወጣ አላቸው።
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ጳጳሳቱ "እግዚአብሔር በዚህ ሕፃን አድሮ ዘለፈን።" እያሉ ለንስሐ በቅተዋል።
ቅዱስ ያዕቆብ ሰባት ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት። በአምስት ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ሊቅ ሆኗል። በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ እርሱ ተሰብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን። አዲስ ምሥጢር ንገረን?" አሉት። እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው።
"እንግዲያውስ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ተርጉምልን?" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል። ፈጣሪንም አመስግነዋል።
ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን፣ ዕጸበ ገዳምን፣ ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል። በድንግልናው ጸንቶ ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል። በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት።) ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል።
በዘመኑም፦
፩.የ፬፻፶፩ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል።
፪.ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል።
፫.በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል።
፬.ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል።
በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በኋላ በተወለደ በሰባ ሁለት ዓመቱ በ፭፻፭ ዓ.ም በዚህች ቀን ዐርፏል። አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ ፳፯ ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ። ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች።
አምላከ ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን።
ሰኔ ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ
፪.ቅዱስ፣ ቡሩክና አሸናፊ አባ አበስኪሮን (ታላቅ ሰማዕትና ባለ ብዙ ተአምራት)
፫.አሥራ ስድስት ሺህ ሰማዕታት (በአንድ ቀን የተገደሉ)
፬.የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የተከፈተበት በዓል (ከአንድ ሺ ዓመታት በፊት ምስር (CAIRO) ውስጥ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
"ይህንን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽህናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው። እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ።"
(፩ጢሞ ፬፥፲፩-፲፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለተባረከ ወር ሐምሌ እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
እግዚአብሔርን ቸር የምንለው በባሕርዩ ፍጹም ቸር በመሆኑ ነው። ይህንን ደግሞ ለማረጋገጥ መቅመስ ይቻላል፤ ይገባልም።
(መዝ. ፴፫፥፯)
ይሔው ደግሞ ያን ሁሉ ኃጢአታችንን ታግሶ ከወርኀ ሐምሌ አደረሰን። ለዚህ ቸርነቱ አምልኮ፣ ውዳሴና ስግደት ይገባዋል።
ለወርኀ ነሐሴ ደግሞ እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል።
<3 ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሊቅ <3
ሐዋርያዊ ጳጳስና ሰማዕት ቅዱስ አግናጥዮስ ገና በልጅነቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያየ ራሱ ጌታችን ትንቢት የተናገረለት (ማቴ. ፲፰፥፩) እና ከጌታ ዕርገት በኋላ ሐዋርያትን የተከተለ አባት ነው። ጌታ ሲያርግ የአምስት ዓመት ሕፃን ሲሆን ከሠላሳ ስድስት ዓመታት በላይ ሐዋርያትንና ቤተ ክርስቲያንን አገልግሏል።
ዕድሜው ወደ አርባዎቹ ሲደርስ ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ዓመት በ፸ ዓ.ም እርሱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሹሟል። አስቀድሞ ከወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ እግር ምሥጢርና ፍቅርን ጠጥቷልና የተለየ ሰው ነበር። ቅዱስ አግናጥዮስ ከአንጾኪያ እየተነሳ ምድረ እስያንም በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሷል።
በአካል ያልደረሰባቸውን በጦማር (በክታብ) አስተምሯል። በአካሉ እንኳ ምንም በጾም፣ በጸሎትና በብዙ ድካም የተቀጠቀጠ ቢሆን ግርማው የሚያስፈራ ነበር። ከነገር ሁሉ በኋላ የወቅቱ ቄሣር ጠራብሎስ ይዞ አሰቃይቶ ለአንበሳ አስበልቶታል። በዚህ ምክንያት "ምጥው ለአንበሳ - ለአንበሳ የተሰጠ" እየተባለ ይጠራል።
<3 አባ ብዮክ እና አባ ብንያሚን <3
እነዚህ ቅዱሳን የሥጋ ወንድማማቾች ናቸው። ካህን አባታቸው በሚገባ ቢያሳድጋቸው እነርሱም ገና በወጣትነት የሚደነቅ የክህነት አገልግሎትን ሰጥተዋል። ሙሉ ሌሊት ለጸሎት፣ ሲነጋ ለኪዳን፣ በሠርክ ደግሞ ለቅዳሴ ይፋጠኑ ነበር። ሁሌም በየቤቱ እየዞሩ የደከመውን ሲያበረቱ፣ የታመመውን ሲፈውሱ፣ ያዘነውን ሲያጽናኑ ውለው ትንሽ ቂጣ ለራት ይመገባሉ።
ሰውነታቸው በፍቅር ሽቱ የታሸ ነበርና ብዙዎችን መለወጥ ቻሉ። አንዴ ቅዳሴ ሊገቡ ሲሉ "አባታችሁ ሊሞት ነው።" ቢሏቸው "ሰማያዊው አባት ይቀድማል።" ብለው ቀድሰዋል። አባታቸውንም ቀብረውታል። በመጨረሻ ግን አንድ ቀን ለመስዋዕት ብለው ያዘጋጁትን የበረከት ሕብስት እባብ በልቶባቸው አገኙ። እንደ ምንም ፈልገው እባቡን ገደሉት።
ነገር ግን ያ የተባረከ ሕብስት በሆዱ ውስጥ ነበርና ምን ያድርጉት? ጌታን ስለ ማክበር ሊበሉት ፈልገው ጌታን ቢጠይቁት መልአኩ መጥቶ "ሰማዕትነት ሆኖ ይቆጠርላችኋል።" አላቸው። ሁለቱ ወንድማማቾች ብዮክና ብንያሚን ፈጣሪያቸውን አመስግነው በሉት። ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ሁለቱንም እንደተቃቀፉ ዐርፈው አገኟቸው። መልካም እረኞቻቸው ናቸውና ከታላቅ ለቅሶ ጋር ቀብረዋቸዋል።
<3 ቅድስት ቅፍሮንያ ሰማዕት ወጻድቅት <3
ይህቺ ቅድስት እናታችን ደግሞ ገና በአሥራ ሁለት ዓመቷ ታላቅ እኅቷን ተከትላ ገዳም ትገባለች። በሚገርም ተጋድሎ በጥቂት ጊዜ አጋንንትን አሳፍራ መነኮሳይያትንም አስገርማቸዋለች። ትጋቷ ግሩም ነበርና ስትታዘዝ ፣ ስትጸልይና ስትሰግድ ያለ እንቅልፍና ምግብ ቀናት ያልፉ ነበር። በዚህ የተቆጣ ሰይጣን አረማዊ መኮንንን ይዞባት መጣ።
ሌሎች ደናግል ሲያመልጡ እርሷ ለመከራ ተዘጋጅታ ጠበቀችው። አዕምሮ የጎደለው መኮንኑም ክርስቶስን ካልካድሽ ብሎ ጽኑዕ ጽኑዕ መከራን አመጣባት። በተጋድሎ ባለቀ አካሏ ሁሉንም ቻለች። በዚህች ቀን ግን አንገቷን በሰይፍ አስቆርጧታል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወዳጆቹን ትዕግስትና ጽናት ለእኛም ያድለን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።
<3 ቅዱስ ቶማስ <3
ዳግመኛ በዚህች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ይታሰባል።
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ። ቅዱስ ቶማስም ያመኑትን "ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሽሹ።" ብሎ መከራቸው።
ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ መሸታ ቤት ይገባል። ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ መሸተኛዋ ሴት እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል ሰይፍ አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት።
እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል። የሠራው ሥራ (መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው። በማግስቱ ቅዱስ ቶማስ ነገሩን ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ ማነው?" ሲል ጠየቀ። ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል ዝም አለ። ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና "ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ።" አለ። ሰውየው ተራውን ጠብቆ ሊያነሳ ሲል እጁ ሰለለች።
ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው። እርሱም እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ። ቅዱስ ቶማስ ግን ሕዝቡ ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን አምጡልኝ።" አለ።
የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል 'የገደልኩሽ እኔ፤ የሚያስነሳሽ ግን ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።' ብለህ አንገቷን ቀጥለው።" አለው። እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች። ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል።
ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን።
ሐምሌ ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሰማዕት
፪.አበው ቅዱሳን ብዮክና ብንያሚን
፫.ቅድስት ቅፍሮንያ (ሰማዕት ወጻድቅት)
፬.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፭.አቡነ ገብረ መድኅን ጻድቅ
፮.አባ ክልዮስ ዘሮሜ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፬.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፭.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
"በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርበው "በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?" አሉት።
ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ። እንዲህም አለ፦ "እውነት እላችኋለሁ። ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።
እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው።" "
(ማቴ ፲፰፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱሳን ነገሥታት ማርቆስ እና ቴዎድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
ማንኛውም ሰው ቢጾም ቢጸልይ፣ መልካም ቢሠራ፣ ለእግዚአብሔር ቢገዛ፣ አልፎም ቢመንን ይደነቃል። ይህንን ሥራ ንጉሥ ሆነው ስለ ሠሩትስ ምን እንላለን? ማድነቅ የሚለው ቃል የሚገልጸው አይመስለኝም።
ወርቅና ብር በእግር እየተረገጠ፣
የሚበላውና የሚጠጣው ተትረፍርፎ ሳለ፣
ሃገር ምድሩ እየሰገደላቸው፣
ሁሉ በእጃቸው
ሁሉም በደጃቸው ሳለ ይህንን ሁሉ ስለ ክርስቶስ ፍቅር የተውት ጻድቃን ነገሥታት የክብር ክብር ይገባቸዋል። ከእነዚህ መካከል ዛሬ የሚከበሩትን ሁለቱን እናዘክር።
<3 ቅዱስ ማርቆስ ንጉሠ ሮም <3
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ቅዱስ ጻድቅ፣ የዋሕ፣ ንጹሕና ገዳማዊ ብላ ትጠራዋለች። ሮም እንደ ዛሬ ጠባብ ከተማ ሳትሆን ዓለምን በክንዷ ሥር ቀጥቅጣ የምትገዛ ኃያል ሃገር ነበረች። ቅዱስ ማርቆስ የልዑላኑ ቤተሰብ ነውና በሮም ተወልዶ በእመቤታችን ቤተ መቅደስ ውስጥ አድጓል።
የየዕለት ሙያው ጾምና ጸሎት መጻሕፍትንም መመልከት ነበር። ነባሩ ንጉሥ ሲሞት መሣፍንቱ ቅዱስ ማርቆስን በድንግልናው ገና ወጣት ሳለ በዚያች ታላቅ ሃገር ላይ አነገሡት። ንጉሥ ቢሆንም ሙሉውን ሌሊት በእመቤታችን ፊት ሲጸልይና ሲያለቅስ ያነጋ ነበር።
ስለ ፍቅርም ድንግል ማርያም ተገልጻ "ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለችው። ቅዱስ ማርቆስም "ለሕዝቡ ፍቅር አንድነትን ሰላምን ስጪልኝ። እኔ በማስተዳድርበት ቦታ ሁሉ ጠብ ክርክር ይጥፋልኝ፤ ፍቅር ይንገስልኝ።" ሲል መለሰላት። ድንግል እመቤታችንም "እንደ ቃልህ ይሁን።" ብላ አጋንንት ወደ ሃገሩ እንዳይገቡ ከለከለችለት። በዚህም ቅዱስ ማርቆስ ከነገሠ ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ጠብ፣ ክርክር፣ ክፋትና ችግር አልነበረም። ሁሉም ተፋቅሮን ያጸና ነበር እንጂ።
ከአምስት ዓመታት በኋላ ግን ሕዝቡና ሹማምንቱ ተሠብስበው አንድ ነገርን መከሩ። ቅዱስ ማርቆስን አጋብተው ለብዙ ጊዜ እንዲመራቸው ማለት ነው። ምክንያቱም አኗኗሩ እንደ መነኮሳት ነውና ጠፍቶ እንዳይሔድ በመስጋታቸው ነው። ከዚያም የሕዝቡ አለቆች ተመርጠው ሃሳባቸውን አቀረቡለት። እርሱ ግን ጭንቅ ሆነበት። ጭራሹኑ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ መጥቶበት አያውቅም።
"እስኪ በጸሎት ላስብበት።" ብሎ መለሳቸው። እነርሱ ግን ወደውታልና ድጋሚ ተሰብስበው ሌላ ነገርን መከሩ። እርሱ ሳያውቅ መልካም ሴት መርጠው ሥርዓተ ተክሊል አዘጋጅተው ድግሱንም አዘጋጅተው በግድም ቢሆን ሊያጋቡት ቆረጡ። ቅዱስ ማርቆስ የተደረገውን ሁሉ ፈጣሪ ገልጦለት በጣም ደነገጠ።
ፈጥኖ ወደ እመ ብርሃን ሥዕል ቀርቦ አለቀሰ። "እመቤቴ! እኔ ከአንቺ ጋር እንጂ ከዚህ ዓለም ጋር መኖር አልችልም።" አላት። እመ ብርሃን ከሰማይ ወደ እርሱ ወርዳ "የምነግርህን ስማኝ። በሌሊት ተነስተህ ወደ ማሳይህ በርሃ ሒድ።" ብላው ተሠወረች። ቅዱስ ማርቆስ ደስ እያለው የንግሥና ልብሱን ጥሎ ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ በሌሊት ከቤተ መንግሥቱ ወጣ።
ወደ ኋላ አልተመለከተም። እመቤታችን እየመራችው ደብረ ቶርማቅ የሚባል በርሃ ውስጥ ባሕር ተከፍሎለት ገባ። ሕዝቡ መልካም እረኛ መሪን አጥቷልና በሮም ከተማ ታላቅ ለቅሶና ሐዘን ተደረገ። ቅዱስ ማርቆስ ግን በደብረ ቶርማቅ በጾም፣ በጸሎትና በተጋድሎ ማንንም ሳያይ ለስልሳ ዓመታት ኖረ።
በዚህች ቀንም ዐርፎ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሒዷል። ሥጋውን የሚቀብር አልነበረምና ከሰማይ ሊቃነ መላእክትና አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ወረዱ። በዝማሬ ሲገንዙትም በድኑ ከመሬት አምስት ክንድ ከፍ ብሎ ተንሳፈፈ።
መላእክቱና ሐዋርያቱም በማኅሌት እዚያው ደብረ ቶርማቅ ውስጥ ቀብረውታል።
<3 ቅዱስ ቴዎድሮስ ንጉሠ ኢትዮጵያ <3
በሃገራችን ታሪክ በጣም ተወዳጅ ከነበሩ ነገሥታት ጻድቁ ቴዎድሮስ ቅድሚያውን ይወስዳል። በርግጥ በርካቶቻችን የምናውቀው ስለ ሃገሩ ፍቅር ራሱን የሰዋውን ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን (፲፰፻፵፭ - ፲፰፻፷) ነው። በበጎ ሥራውና በቅድስና ሕይወቱ የተመሠከረለት ግን ዛሬ የምናስበው ቀዳማዊው ነው።
ቀዳማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የደጉ ዐፄ ዳዊት (ግማደ መስቀሉን ያመጡት) እና የተባረከችው ሚስታቸው ጽዮን ሞገሳ ልጅና የጻድቁ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ታላቅ ወንድም ነው።
በኢትዮጵያ ለሦስት ዓመታት (ከ፲፫፻፺፮ - ፲፫፻፺፱) ብቻ ነግሦ እያለ እንደ ንጉሥ ሳይሆን
ከጠዋት እስከ ማታ ድሃ እንዳይበደል ፍርድ እንዳይጓደል ይታትር የነበር፣
ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር፣
ወገቡን ታጥቆ ነዳያንን የሚያበላ፣
ለአብያተ ክርስቲያናትም የሚጨነቅ ደግ ሰው ነበር።
ስለዚህም በሕዝቡ እጅግ ተወዳጅ ነበር። በነገሠ በሦስት ዓመቱ ዐርፎ በዝማሬና በለቅሦ ሥጋውን ተሸክመው ሲሔዱ ወንዝ ተከፍሎላቸዋል። ከመቃብሩም ላይ ጠበል ፈልቋል።
ቸር አምላክ መልካም መሪ ለሃገራችን በጐ እረኛንም ለነፍሳችን ያድለን። ከቅዱሳን ነገሥታቱም ጸጋ በረከትን ይክፈለን።
ሰኔ ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ንጉሠ ሮም (ጻድቅ፣ ንጹሕና ገዳማዊ)
፪.ቅዱስ ቴዎድሮስ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፫.ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ኢትዮጵያዊ (ፍልሠቱ)
፬.ሰባቱ ቅዱሳን መስተጋድላን (አባ አብሲዳ፣ አባ ኮቶሎስ፣ አባ አርድማ፣ አባ ኒኮላስ፣ አባ ሙሴ፣ አባ እሴይና አባ ብሶይ)
፭.ቅዱሳን አባ ሖር፣ አባ ብሶይ፣ አባ ሖርሳና እናታቸው ቅድስት ይድራ (ሰማዕታት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪.ቅድስት አርሴማ ድንግል
፫.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፭.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊት
፮.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
"አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል። በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል።
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው። የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም።
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና። ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ።
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም። ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ።
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው።"
(መዝ ፳፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ እና ለሰማዕቱ ቅዱስ ቶማስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ <3
ሐናንያ ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ከተቀመጠልን ከጥቂቶቹ ዋነኛው ነው። ከነገደ እስራኤል ተወልዶ በሕገ ኦሪት አድጐ ከወጣትነት ዕድሜው ትንሽ እልፍ ሲል ጌታችን ወንጌልን ማስተማር ጀምሯልና ጠራው። እርሱም በበጐ ፈቃድ ተከትሎታልና ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደመረው።
ለሦስት ዓመታት ከጌታ እግር ተምሮ ከዕለተ ስቅለት በፊት ሃብተ ፈውስም ተሰጥቶት ነበር። ምክንያቱም ቅዱስ ሉቃስ እንደ ጻፈልን ሰብዐው አርድእት "ጌታ ሆይ! አጋንንት በስምህ ተገዙልን።" ማለታቸውን አስቀምጦልናል።
(ሉቃ. ፲፥፲፯)
ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በሃምሳኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል።
በሚያስተምር ጊዜ የሶርያዋን ደማስቆን ማዕከል አድርጐ ነበር። በኋላም አበው ሐዋርያት የዚህች ከተማ የመጀመሪያው ጳጳስ አድርገው ሹመውታል። ጌታ ባረገ በስምንተኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ የነበረው ሳውል (የኋላው ቅዱስ ጳውሎስ) ወደ ደማስቆ የተጓዘው ክርስቲያኖችን በተለይም ቅዱስ ሐናንያን ለማሠር ነበር።
ለእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ ይሆን ዘንድ መብረቅ ዓይኑን አጠፋው። ወዲያውም ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሔድ ነገረው። ከሦስት ቀናት በኋላ ጌታችን ለሐናንያ ተገልጦ አነጋግሮታል።
ሳውል (ጳውሎስ) ወደ ሐናንያ የደረሰው በመሪ ነበር። ሁለቱ እንደተገናኙ ቅዱስ ሐናንያ ሳውልን አስተማረው፣ ፈወሰው፣ አጠመቀው፣ በጐ መንገድንም መራው። በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ሐዋርያ የቅዱስ ጳውሎስ የንስሐ አባቱ ይሰኛል።
(ሐዋ. ፱፥፩-፲፱)
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን አስተማረ። መከራንም ተቀበለ። በመጨረሻም በዚህ ቀን ክፉዎች ከብዙ ስቃይ በኋላ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል።
<3 ቅዱስ ቶማስ ዘሰንደላት <3
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩ ሰማዕታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ወደ ሰማዕትነት ሕይወት የገባው በአሥራ አንድ ዓመቱ በመላእክት መሪነት ነው። ገና ወደ ምስክርነት አደባባይ እንደ ቀረበ መኮንኑ "ክርስቶስን ካድና ልሹምህ።" ቢለው ሕፃኑ ቅዱስ ቶማስ ተቆጥቶ "አንተ ሰነፍ መኮንን" ብሎ ገስጾ በጐችን ይመልስባት በነበረችው ጅራፍ ገርፎታል። ይሔም በዘመኑ የመጨረሻው የድፍረት ደረጃ ነበር።
በዚህም ምክንያት በሕፃን ገላው ላይ የተቀበለው መከራ ሊናገሩት ይከብዳል።
ግርፋት፣ እሳትና አራዊት በእርሱ ላይ አልፈዋል። አካሉም ተቆራርጧል። አንድ ጊዜም "ለጣዖታችሁ እንድሰግድ አምጡት።" ብሏቸው ልክ ከፊቱ ሲደርሱ ወደ ጌታ ቢጸልይ መሬት ተከፍታ ውጣቸዋለች።
እርሱን ያሰቃየው የነበረውን መኮንንም ከደዌው አድኖ ከነ ሠራዊቱ አሳምኖታል። ሕፃኑን ቅዱስ ቶማስን ግን ያላመኑ አረማውያን በዚህች ቀን አንገቱን ሰይፈውት በሰማዕትነት ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔዷል።
አምላከ ቅዱሳን ከሐዋርያው በረከት ከሰማዕቱም ምልጃ አይለየን።
ሰኔ ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
፪.ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት (ዘሰንደላት)
፫.ቅዱስ አልዓዛር ነዳይ (በነዌ ደጅ የወደቀ ቀጥሎ ደግሞ በአብርሃም እቅፍ ውስጥ የተገኘ ጻድቅ)
፬.ቅዱስ ማማስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪.አቡነ መብዐ ጽዮን ጻድቅ
፫.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፮.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
"በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ። ጌታም በራእይ "ሐናንያ ሆይ!" አለው። እርሱም "ጌታ ሆይ! እነሆኝ።" አለ። ጌታም ተነስተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሒድ። በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ። እነሆ እርሱ ይጸልያልና። ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቷል።" አለው።"
(ሐዋ ፱፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ከዘመነ ጸደይ ወደ ዘመነ ክረምት መሸጋገሪያ ለሆነችው ዕለትና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
ስንዱ እመቤት ቤተ ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች። እሊሕም ዘመናት መጸው (ጽጌ)፣ ሐጋይ (በጋ)፣ ጸደይ (በልግ)ና ክረምት ናቸው። ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል።
በተለይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና "ሽሽታችሁ (ስደታችሁ) በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ።" ብሎናልና (ማቴ. ፳፬፥፳) ልንጸልይ ይገባናል።
በዘመነ ክረምት ቅጠል እንጂ ፍሬ የለበትምና ፍሬ ምግባር ሣናፈራ ሞት እንዳይመጣ።
አንድም ክረምት የዝናብና የጭቃ ጊዜ በመሆኑ እንኳንስ ለስደት ለኑሮም አይመችምና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጸልይ፦
"በዝንቱ ክረምት በመዋዕሊነ።
ዘእንበለ ፍሬ እንዘ በቆጽል ኀሎነ።
ናስተበቁዐከ እግዚኦ ኢይኩን ጉያነ።"
(ክረምት በተባለ በእኛ እድሜ ፍሬ ሳናፈራ በቅጠል /ያለ መልካም ሥራ/ ሳለን አቤቱ ጌታ ሆይ ስደትን አታምጣብን።)
ቸሩ አምላካችን ከዘመነ መጸው በሰላም ያድርሰን። ተረፈ ዘመኑንም የንስሐ፣ የፍሬና የበረከት ያድርግልን።
<3 ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ <3
በዘመነ ሐዋርያት ይሁዳ ተብለው ይጠሩ ከነበሩት አንዱ የሆነው ቅዱሱ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ ሲሆን እናቱ ማርያም ትባል ነበር። እናቱ ስትሞትበት ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ገና በልጅነቱ ድንግል ማርያም አግኝታው በፍጹም ጸጋ አሳድጋዋለች። አስተዳደጉም ከጌታችን ጋር በአንድ ቤት ነበር።
ጌታችን እርሱንና ወንድሞቹን (ያዕቆብና ስምዖንን) ከሰባ ሁለቱ አርድእት ቆጥሯቸዋል። ቅዱስ ይሁዳ ወንጌል ላይ ከጌታችን ጋር መነጋገሩን ዮሐንስ ወንጌላዊ መዝግቧል።
(ዮሐ. ፲፬፥፳፪)
ቅዱስ ይሁዳ ከጌታችን እግር ሦስት ዓመት ተምሮ መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ ብዙ አሕጉራትን ዙሯል። አይሁድንም አረማውያንንም ወደ ክርስቶስ ይመልስ ዘንድ ብዙ ድካምና ስቃይን በአኮቴት ተቀብሏል። አንዲት አጭር (ባለ አንድ ምዕራፍ) መልእክትም ጽፏል። አጭር ትምሰል እንጂ ምሥጢሯ እጅግ የሠፋ ነው።
ቅዱስ ይሁዳን በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውት በሐዋርያነቱ ላይ የሰማዕትነትን ካባ ደርቧል።
<3 ቅዱሳን ጲላጦስና አብሮቅላ <3
ብዙዎቻችን መስፍኑን ጲላጦስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን እንዳይሰቀል ከአይሁድ ጋር ሲከራከር እናውቀዋለን። የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ ነበርና አይሁድ እንቢ ሲሉት የክርስቶስን ንጽሕና መስክሮ እጁንም ታጥቦ ሰጥቷቸዋል። የጲላጦስ ታሪክ ግን እዚህ ላይ አያበቃም።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በኋላ ትንሣኤውን በራእይ ገልጦለት አይሁድን ተከራክሯቸዋል። ውሸታም ወታደሮችንም ቀጥቷል። በመጨረሻ ግን በሮም ቄሳር ተጠርቶ ከእስራኤል እስከ ሮም ድረስ ሰብኮ በሮም አደባባይ አንገቱ ተሠይፏል።
ቅድስት እናታችን አብሮቅላም የጲላጦስ ሚስት ስትሆን ቁጥሯ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ነው። ጌታችንን ተከትላ ቤቷን ለሐዋርያት አስረክባ ቤተ ክርስቲያንንም በዘመኗ አገልግላ ዐርፏለች። ዛሬ ሁለቱም ቅዱሳን ይታሠባሉ።
ጌታችን ከሐዋርያው ይሁዳ፣ ከጲላጦስና አብሮቅላም ጸጋ በረከትን ያድለን።
ሰኔ ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
፪.ሰማዕቱ ጲላጦስ መስፍን
፫.ቅድስት አብሮቅላ (ሚስቱ)
፬.አባ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፮.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
"የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ።
ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ።
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።"
(ይሁዳ ፩፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
"ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ እምዕንቈ ባሕርይ ዘየሐቱ
ዘተጽሕፈ ብኪ ትእምርተ ስሙ ወተዝካረ ሞቱ
አክሊለ ጽጌ ማርያም ለጊዮርጊስ ቀጸላ መንግሥቱ
አንቲ ኲሎ ታሰግዲ ሎቱ
ወለኪኒ ይሰግድ ውእቱ።"
(የስሙና የሞቱ መታሰቢያ ባንቺ የተጻፈብሽ የሚያበራ ከሆነ ዕንቈ ባሕርይ ይልቅ የጠራ ወርቅ ክበብ ያለው የራስ ቊር የተባለ የጊዮርጊስ የመንግሥቱ የራስ ልብስ ጌጥ ሽልማት የአበባ አክሊል ማርያም ሆይ አንቺ ለእርሱ ሁሉን ታሰግጅለታለሽ (ታንበረክኪለታለሽ) እርሱ ግን ላንቺ ይሰግዳል።)
(አባ ጽጌ ድንግል)
እንኳን ለቅዱሱ አባታችን የዋህ ጳውሊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ጳውሎስ የዋህ <3
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ግብጽ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ቅዱሱ ስሙ ጳውሎስ ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚጠራው "የዋህ ጳውሊ" በሚል ነው።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
የዋህ ጳውሊ ከሕፃንነቱ ጀምሮ መጻሕፍትን የተማረ ግን ደግሞ ትዕቢት፣ ቁጣና ቂምን የማያውቅ ገራገር ሰው ነው። እድሜው ለአካለ መጠን ሲደርስ ቤተሰቦቹ ሚስት አግባ አሉት። እርሱ ባያስብበትም ወገኖቹን ላለማሳዘን አገባ።
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ያገባት ሴት በጣም ቆንጆ በዚያም ላይ ክፉ ነበረች። የዋህ ጳውሊ ክፋቷን ሁሉ ታግሶ ለበርካታ ዓመታት አብሮ ኖረ፤ ልጆችንም አፈሩ። አሁንም ግን እርሷ ከክፋቷ ልትታገስ አልቻለችም። ይባስ ብሎ ጳውሊ በሌለበት ከሌሎች ወንዶች ጋር ትዘሙት ያዘች።
የዋሁ ሰው ይህንኑ ያውቃል። ግን የእግዚአብሔርን ሥራ ዝም ብሎ በተስፋ ይጠብቅ ነበር።
ለነገሩስ እርሱ
ያርሳል፣ ይቆፍራል፣ ነዳያንን ያበላል፣ እንግዳ ይቀበላል እንጂ ክፋትን ለማሰብ ጊዜ አልነበረውም።
አንድ ቀን ግን ለሥራ ወደ በርሃ ወጥቶ አንድ ግሩም ዜና ሰማ። "አባ እንጦንስ ምንኩስና የሚባል ሕይወተ መላእክትን ጀምሯል። ደቀ መዛሙርትንም ይቀበላል።" አሉት። ግን ሚስትና ልጆች አሉትና ምን ያደርጋል?
የዋህ ጳውሊ ሙሉ ቀን ሢሠራ ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ግን የጠበቀው ሌላ ነው። ሚስቱ በራሱ መኝታ ላይ ከአገልጋይ እረኛው ጋር ራቁታቸውን አገኛቸው። ልብ በሉልኝ! በትክሻው ሞፈር፣ ምሳርና መጥረቢያ ይዟል። እርሱ ግን ክፉን አላሰበም። ጥሩ ልብስ አንስቶ ሁለቱንም አለበሳቸው።
እንዲህም አላቸው፦ "ከዚህ በኋላ እኔ አልመለስም። ሀብት ንብረቴን ውረሱ። በደስታም ኑሩ። የልጆቼን ነገር ግን አደራ።" ብሏቸው ተነሳ።
በእጁ ምንም አልያዘም። በትከሻው ያለችውን ብጣሽ ጨርቅ ይዞ ወደ በርሀ ተጓዘ። አባ እንጦንስም ተቀብለው አስተምረው አመነኮሱት። ከዚያች ቀን ጀምሮ ራስን ዝቅ በማድረግ በመታዘዝ አገለገለ። ጾም፣ ጸሎትና ስግደቱንማ ማን ቆጥሮት።
እያለ እያለ ከብቅዐት ማዕርግ ደረሰ። ምዕመናንም ሆነ መነኮሳት ሊጠይቁት ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይመለከት ነበርና ስለእነርሱ ሲያለቅስ ቅንድቡ ተላጠ፤ ሰውነቱም አለቀ።
አንድ ቀን ጋኔን የያዘውን ሰው ፈውስ ብለው አመጡለት። በአጋንንት ላይ ሥልጣን እያለው እርሱ ግን በትሕትና ተጠግቶ ጋኔኑን "አባ እንጦንስን ከምጠራብህ ቀስ ብለህ ውጣ!" አለው። ጋኔኑ ግን የፈራው መስሎት በትዕቢት "እንጦንስ ማነው?" አለው።
ያን ጊዜ የዋህ ጳውሊ እንደ እሳት ከጋለ ድንጋይ ላይ ቁሞ "ሕያው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ይህ ጋኔን ካልወጣ አልወርድም።" አለ። ወዲያው ያ ጋኔን በዘንዶ አምሳል ከሴትዮዋ ወጥቶ እየጮኸ ወደ ቀይ ባሕር ገባ። ቅዱስ ጳውሊ የዋሕም እንዲህ በቅድስና ተመላልሶ በዚህች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።
አምላካችን ከቅዱስ ጳውሊ የውሃትን፣ ትእግስትን፣ በጐነትን፣ ጸጋ በረከትን ይክፈለን።
ሰኔ ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ጳውሊ የዋሕ
፪.ቅዱሳን ወክቡራን ቆዝሞስና ድምያኖስ (ሰማዕታት)
፫.ቅድስት ቴዎዳዳ ሰማዕት (እናታቸው)
፬.አንቲቆስ፣ ዮንዲኖስና አብራንዮስ (ሰማዕታት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፬.አባ እንጦንዮስ (አበ መነኮሳት)
"የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትእግስት፣ ቸርነት፣ በጐነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።"
(ገላ ፭፥፳፪-፳፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያን <3
ትናንት ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሐዋርያት ወረደ። ፊልጵስዩስ በምትባል ሃገር በጴጥሮስ እጅ የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን አነጸ ብለን ነበር። በዚህች ዕለት ደግሞ አእላፍ መላእክትን፣ ሰማያውያን ቅዱሳንንና እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዟት ወረደ።
ሐዋርያቱ አብዛኞቹ እዚያው ሲጸልዩ አድረው ነበርና ጌታችን ከቅዳሴው በፊት ሁለት ነገሮችን አሳየ።
፩.አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያኗን በድንግል እናቱ ስም አክብሮ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አሳየ።
፪.ቀጥሎ ደግሞ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን ከመካከል አቁሞ "አርሳይሮስ" ሲል ሾመው። ይኼውም የዓለም ሁሉ ሊቀ ጳጳሳት (ፓትርያርክ) ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት "አክዮስ" እያሉ ሦስት ጊዜ አሰምተው ጮሁ። "አክዮስ" ማለት በግዕዙ "ይደልዎ"፣ በዐማርኛው ደግሞ "ይገባዋል፤ ያሥምርለት።" እንደ ማለት ነው።
ጌታችን ይህን ከከወነ በኋላ ይቀድስ ዘንድ ጀመረ።
አማናዊት ማኅደሩን ድንግል ማርያምን መንበር አድርጎ፣
ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተራዳኢ ካህን ቆሞ፣
ቅዱስ እስጢፋኖስ ሠራኢ ዲያቆን ሆኖ፣
ሐዋርያት ድንግልን ከበው፣
መላእክተ ብርሃን በክብራቸው ቁመው ጌታችን ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወዳጆቹ አቀበለ።
በዚያች ዕለት በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይችል ደስታ ተደረገ። ከቅዳሴ በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን አዘዛቸው።
"ከዚህች ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም በእናቴ በማርያም ስም አብያተ ክርስቲያናትን አንጹ። ይህችን ዕለት የሚያከብራትን አከብረዋለሁ።" ብሏቸው ከድንግል እናቱ፣ ከመላእክቱ ጋር ዐረገ።
<3 ሰኔ ጐልጐታ <3
በሌላ በኩል ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም በዚህ ቀን (ሰኔ ፳፩) ልጇን ወዳጇን ጐልጐታ ላይ ለኃጥአን ምሕረትን ለምናዋለች። ጌታችንም "ስምሽን የጠራውን፣ በቃል ኪዳንሽ ያመነውን ሁሉ እምርልሻለሁ።" ብሏታል።
የድንግል እመቤታችን ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ጣዕመ ፍቅሯና በረከቷ በሁላችን ላይ ይደርብን።
<3 ቅዱስ ቶማስ <3
ዳግመኛ በዚህች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ይታሰባል።
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ። ቅዱስ ቶማስም ያመኑትን "ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሽሹ።" ብሎ መከራቸው።
ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ መሸታ ቤት ይገባል። ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ መሸተኛዋ ሴት እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል ሰይፍ አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት።
እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል። የሠራው ሥራ (መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው። በማግስቱ ቅዱስ ቶማስ ነገሩን ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ ማነው?" ሲል ጠየቀ። ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል ዝም አለ። ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና "ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ።" አለ። ሰውየው ተራውን ጠብቆ ሊያነሳ ሲል እጁ ሰለለች።
ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው። እርሱም እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ። ቅዱስ ቶማስ ግን ሕዝቡ ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን አምጡልኝ።" አለ። የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል 'የገደልኩሽ እኔ፤ የሚያስነሳሽ ግን ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።' ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው። እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች። ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል።
ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን።
ሰኔ ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
፪.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
፫.ቅዱሳን ሐዋርያት
፬.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፭.ቅዱሳን ጳውሎስና በርናባስ
፮.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፯.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፰.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘምስር (ሰማዕት)
፱.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ጳጳሳት
ወርኀዊ በዓላት
፩.አበው ጎርጎርዮሳት
፪.አቡነ ምዕመነ ድንግል
፫.አቡነ አምደ ሥላሴ
፬.አባ አሮን ሶርያዊ
፭.አባ መርትያኖስ ጻድቅ
"ስለ ጽዮን ዝም አልልም።
..... አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ። የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።"
(ኢሳ ፷፪፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ሕንጸተ ቤታ (ሕንጸታ) በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 በዓለ ሕንጸታ <3
በዚህች ቀን በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በአምላክ እናት ስም ታንጻለች።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን "ሑሩ ወመሐሩ ኩሎ አሕዛበ - አሕዛብን ሁሉ ሒዱና አስተምሩ።" (ማቴ. ፳፰፥፲፱) ባላቸው ቃል መሠረት ዓለምን በወንጌል ያርሷት ዘንድ በዕጣ ተካፍለዋታል።
የሰው ልጅ ድኅነቱ የሚፈጸመው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበል ነውና።
(ዮሐ. ፮፥፶፮)
አበው ሐዋርያት ቁርባንን በተመረጡ ሰዎች ቤት እያዘጋጁ ቀድሰው ያቆርቡ ነበር።
በመጀመሪያ በጽርሐ ጽዮን ቀጥሎም በተለያዩ ሰዎች ቤት እንዲህ ይከናወን ነበር። ለጸሎት ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ምኩራበ አይሁድን ይጠቀሙ ነበር። እየቆየ ሲሔድ ግን ከአሕዛብ ያመኑ ሰዎች ቁጥር እጅጉን በዛ።
በተለይ ቅዱስ ጳውሎስ ያሳመናቸው ለጸሎት እያሉ ወደ ጣዖት ቤት መግባት አመጡ። በዚህ ምክንያት መምሕራን ሕዝቡን "ካመናችሁ በኋላ እንዴት ወደ ጣዖት ቤት ትገባላችሁ?" ቢሏቸው "እኛ ምን እናድርግ! የምንጸልይበት እንደሆን የለን።" ሲሉ መለሱላቸው።
ነገሩ ሲያያዝ ከደጋጉ ሐዋርያት ጳውሎስና በርናባስ ደረሰ። ወዲያውኑ አንዳንድ ወንድሞች "ለምን አናንጽም።" ብለው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ግን "ሊቀ ሐዋርያቱ ሳይፈቅድ አይሆንም።" አለ። (ለዚህ ነው ዛሬም ሊቀ ጳጳስ ካልፈቀደ ቤተ ክርስቲያን የማይታነጸው።)
ከዚያ ቅዱሳን ጳውሎስና በርናባስ ሐዋርያቱ ወዳሉበት ሔደው ነገሩን ለቅዱስ ጴጥሮስ አስረዱ። ሊቀ ሐዋርያቱም "የጌታችን ፈቃዱ መሆኑን እናውቅ ዘንድ ተያይዘን ሱባዔ እንግባ።" ብሎ አዋጅ ነገረ።
በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በአንድ ልብ ሱባዔ ገቡ። በሱባዔአቸው መጨረሻም ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ ወደ እነርሱ ወረደ።
ሁሉንም ሐዋርያት በደመና ጭኖ ፊልጵስዩስ አደረሳቸው። ከከተማ ወጣ ብሎ ባለ መሬት ላይም "ቤተ ክርስቲያንን በእናቴ ስም አንጹ።" ብሎ አዘዛቸው። ለቅዱስ ጴጥሮስም ሦስት ዓለቶችን ሰጠው።
እነዚያን መሬት ላይ ተክሎ ጌታችን ቆሞለት ሐዋርያቱ እየተራዱት ግርምት የምትሆን ሦስት ክፍል ያላትን የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን በ፶፪ ዓ.ም በዚህች ቀን አንጿል።
ቤተ ክርስቲያኗን ነገ ጌታችን ቀደሳት የምንል ነንና ይቆየን።
አምላካችን የድንግል እናቱን ፍቅር የተቀደሰች ቤቱን ጸጋ የቡሩካን ሐዋርያቱን በረከት ያሳድርብን።
ሰኔ ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
፪.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
፫.ቅዱሳን ሐዋርያት
፬.ቅዱስ ኤልሳዕ ነቢይ (ዕረፍቱ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፫.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፬.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፭.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፮.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
"በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሠር አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።
..... የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።"
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድምያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አባ ድምያኖስ <3
አባ ድምያኖስ ተወልደው ያደጉት ግብጽ ውስጥ ነው። ቤተሰቦቻቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ገና በልጅነት ዕድሜአቸው ቅዱሳት መጻሕፍትንና በጐ ምግባራትን ተምረዋል። ዕድሜአቸው ወደ ወጣትነቱ ሲጠጋ ሥርዓተ መነኮሳትን ለማጥናት ወደ ገዳመ አባ ዮሐንስ ሔዱ። በዘመኑ ማንኛውም ሰው ተገቢውን ፈተና ሳያልፍ እንዲመነኩስ አይፈቀድለትም ነበር።
አንድ ሰው ሊመነኩስ ካሰበ በትክክል መናኝ መሆኑ ቢያንስ ለሦስት ቢበዛ ደግሞ ለአሥራ ሁለት ዓመታት እንዲፈተን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታዝዛለች። ይኸውም "ሥርዓተ አመክሮ" ይባላል። ከአሥራ ሁለት ዓመታት በላይ መቆየት ከፈለገ ግን ይፈቀድለታል።
በዚህም መሠረት አባ ድምያኖስ ለአሥራ ሰባት ዓመታት በአጭር ታጥቀው ገዳሙን አገልግለዋል። ገዳሙም ይገባሃል በሚል ዲቁና እንዲሾሙ አድርጓል። ከዚህ በኋላ ከአባቶች ተባርከው ገዳሙንም ተሰናብተው ወጡ። ነገር ግን የወጡት ወደ ዓለም ሳይሆን ራቅ ወዳለ ገዳም ነው።
የረድዕነት ዘመናቸውን ጨርሰዋልና አዲስ በሔዱበት ገዳም ወደ መደበኛው ገድል ተሸጋገሩ። ያም ማለት በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በትሕርምት፣ በትሕትናና በፍቅር ሙሉ ጊዜአቸውን ማሳለፍ ጀመሩ። በእንዲህ ያለ ግብርም ዘመናት አለፉ።
የወቅቱ የግብጽ ፓትርያርክ አባ ጴጥሮስ በእረኝነት ሥራ የሚያግዛቸው ሰው እንዲፈለግላቸው በጠየቁት መሠረት ትምህርትም፣ ጽሕፈትም፣ በጐ ምግባራትም የተሟላለት ሰው እንደ አባ ድምያኖስ አልተገኘምና ያለፈቃዳቸው ወደ እስክንድርያ ተወስደው የፓትርያርኩ ረዳት ሆነው ተሾሙ። በረዳትነት በቆዩበት ጊዜ በወንጌል አገልግሎትና በመንኖ ጥሪት ሕዝቡንና ሊቀ ጳጳሳቱን አስደስተዋል።
ልክ አባ ጴጥሮስ ሲያርፉ ሕዝቡና ሊቃውንቱ በአንድ ድምጽ አባ ድምያኖስን ለፓትርያርክነት መርጧቸዋል።
ጻድቁ ሊቀ ጳጳሳት በዘመነ ፕትርክናቸው ከግል የቅድስና ሕይወታቸው ባለፈ እነዚህን ፈተናዎች በመወጣታቸው ይመሰገናሉ።
፩.ሕዝቡ ከሃይማኖታቸው እንዳይወጡና በምግባር እንዳይዝሉ ተግተው አስተምረዋል።
፪.በአካል ያልደረሱባቸውን በጦማር (በመልእክት) አስተምረዋል።
፫.በዘመናቸው የተነሱትን መናፍቃን ተከራክረው የተመለሰውን ተቀብለው እንቢ ያሉትን አውግዘዋል።
፬.ከአንጾኪያ ፓትርያርክ የመጣውን የኑፋቄ ጦማር (መልእክት) በይፋ ተቃውመው አውግዘዋል።
ለአርባ ሦስት ዓመታት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሆነው ያገለገሉት አባ ድምያኖስ ከብዙ ትጋት በኋላ በመልካም ሽምግልና በዚህች ቀን ዐርፈዋል። ከግብጽ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ዝርዝር ውስጥም አርባ አምስተኛ ሆነው ተመዝግበዋል።
ልመናቸው፣ ክብራቸው፣ ጸጋ ረድኤታቸው አይለየን።
ሰኔ ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ድምያኖስ ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
፫.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
"ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ..... እኔ አውቃለሁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።"
(ሐዋ ፳፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለታላቁ ገዳማዊ አባ አቡናፍር ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ አቡናፍር ገዳማዊ <3
ጻድቁ ተወልዶ ያደገው በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ነው። ወቅቱ ሥርዓተ መነኮሳት የሚጠበቅበት አበው ባሕታውያን እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝተው የደመቁበት ነበር። ታላቁ አቡናፍርም ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ፣ በሥርዓት አድጎ፣ መጻሕፍትንም ተምሮ ገና በወጣትነቱ መንኗል።
ሥርዓተ መነኮሳትን ከአባ ኤስድሮስ ታላቁ አጥንቶ ገዳሙንና መምህሩን እየረዳ ለብዙ ዓመታት በጾምና በጸሎት ኑሯል። መነኮሳቱ ስለ ትሕትናውና ስለ ታዛዥነቱ ፈጽመው ያከብሩት ነበር።
ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋውያን መነኮሳት ጭው ባለ በርሃ ስለሚኖሩ ባሕታውያን ሲጨዋወቱ ሲያደንቋቸውም ሰማ። እርሱ በዚያ ወቅት ባሕታውያን በበርሃ መኖራቸውን አያውቅም ነበርና ሒዶ መምህሩን አባ ኤስድሮስን ጠየቃቸው። እርሳቸውም "አዎ ልጄ! ከዚህ በጣም ርቅው፣ ንጽሕናቸውን ጠብቀው፣ ከሰውና ከኃጢአት ተይለው የሚኖሩ ገዳማውያን አሉ።" አሉት።
ቅዱስ አቡናፍር "በዚህ ካሉት መነኮሳትና በበርሃ ካሉት ማን ይበልጣል?" ቢላቸው "እነርሱ በጣም ይበልጣሉ። ዓለም እንኳ ከነ ክብሯ የእግራቸውን ሰኮና አታህልም።" አሉት። ይህንን የሰማው ቅዱስ አባ አቡናፍር ጊዜ አላጠፋም።
ከመምህሩ ቡራኬ ተቀብሎ ወደ በርሃ ሔደ። ለብዙ ቀናት ከተጓዘ በኋላ አንድ ባሕታዊ አግኝቶ አብሯቸው ተቀመጠ። ከእርሳቸው ዘንድም ሥርዓተ ባሕታውያንን ተምሮ እንደገና ወደ ዋናው በርሃ ጉዞውን ቀጠለ።
ከብዙ ቀናት መንገድ በኋላም አንድ ሠፊ ሜዳ ላይ ደረሰ። አካባቢው የውኃ ጠብታ የማይገኝበት ይቅርና መጠለያ ዛፍ የሣር ዘር እንኳ የሌለበት ወይም በልሳነ አበው
"ዋዕየ ፀሐይ የጸናበት፣ ልምላሜ ሣዕር የሌለበት፣ ነቅዐ ማይ የማይገኝበት" ቦታ ነበር። በዚህ ቦታ ይቅርና የሰው ልጅ አራዊትም አይኖሩበትም።
ለአባ አቡናፍር ግን ተመራጭ ቦታ ነበር። ቅዱሳኑን ይህ አያሳስባቸውም። ምክንያቱም ለእነርሱ ምግባቸውም ልብሳቸውም ፍቅረ ክርስቶስ ነውና። አባ አቡናፍር ወደ ፈጣሪ ጸለዩ። በእግዚአብሔር ቸርነት ከጎናቸው አንዲት ዘንባባ (በቀልት) በቀለች። ከእግራቸው ሥርም ጽሩይ ማይ (ንጹሕ ምንጭ) ፈለቀች።
ጻድቁ ተጋድሏቸውን ቀጠሉ፤ ዓመታት አለፉ። ልብሳቸውን ፀሐይና ብርድ ጨርሶት ቅጠል ለበሱ። በዚያ ቦታም የሰው ዘርን ሳያዩ ለስልሳ ዓመታት በተጋድሎ ኖሩ። የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አባ በፍኑትዮስን (የባሕታውያንን ዜና የጻፈ አባት ነው።) ላከላቸው።
ቃለ እግዚአብሔርን እየተጨዋወቱ ሳለ የአባ አቡናፍር አካሉ ተለወጠ። እንደ እሳትም ነደደ። አባ በፍኑትዮስም ደነገጠ። ታላቁ ገዳማዊ ግን እጆቻቸውን ዘርግተው ጸለዩ፣ ሰገዱና አማተቡ። ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በዝማሬና በማኅሌት አሳረጓት። የሚገርመው ደግሞ አባ በፍኑትዮስ ይህን ሲያይ ቆይቶ ዘወር ቢል ዛፏ ወድቃለች። ምንጯም ደርቃለች።
ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱሳን አበው ባሕታውያን መታሠቢያ ናት።
ከሰው (ከዓለም) ርቀው፣ ንጽሕ ጠብቀው፣ ዕጸበ ገዳሙን፣ ግርማ አራዊቱን፣ ጸብዐ አጋንንትን ታግሠው የኖሩ ስማቸውን የምናውቀውንም ሆነ የማናውቃቸውን እንድናከብራቸው ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና በዓል ሠርታለች።
አምላካችን ከአበው ባሕታውያን ጸጋ በረከት ይክፈለን።
ሰኔ ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.አባ አቡናፍር ገዳማዊ (ስም አጠራሩ የከበረ፣ ሽምግልናው ያማረ አባት)
፪.አበው ቅዱሳን ባሕታውያን
፫.የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ከግብጽ እንዲመለስ የነገረበት (ተዝካረ ሚጠታ ለእግዝእትነ ማርያም)
፬.አፄ ይኩኖ አምላክ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
፬.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፮.አባ ዳንኤል ጻድቅ
"..... ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእሥራትና በወኅኒ ተፈተኑ።
ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ፣ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፮-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለአራቱ ቅዱሳን አበው ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አበው ሰማዕታት <3
አራቱ ቅዱሳን አበው የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ሲሆኑ ስማቸው አባ አክራ፣ አባ ዮሐንስ፣ አባ አብጥልማ እና አባ ፊልጶስ ይባላሉ። ከመከራ ዘመን በፊት (ማለትም በቀደመ ሕይወታቸው) ካህናትና ሃብታሞች ነበሩ። ሀብቱ ግን በሥራ ብቻ የተገኘ ነው።
ታዲያ ቅዱሳኑ በያሉበት ሆነው በሀብታቸው እንግዳ እየተቀበሉ፣ ድሆችን እያበሉ፣ በክህነታቸው ደግሞ እያስተማሩና እየናዘዙ ትጉሃን ስለ ነበሩ በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ነበራቸው። በእንዲህ ያለ ግብር ሳሉ ዘመነ ሰማዕታት አሐዱ አለ። "ክርስቶስን ካዱ፤ ለጣዖት ስገዱ።" እያሉ መኳንንቱና ነገሥታቱ ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሰቃዩ ገቡ።
በዚህ ጊዜ አራቱ ቅዱሳን አንድ ነገር መከሩ። በየእሥር ቤቱ የተጣሉ ክርስቲያኖችን ለማገልገል ቆረጡ። እግረ መንገዳቸውን እያስተማሩ እሥረኞችን ያጽናኑ ገቡ። የራበውን ያበላሉ። የተሰበረውን ይጠግናሉ። በቁስሉም ላይ መድኃኒትን ያደርጉ ነበር። የመከራው ዘመን ግን እየረዘመ ግፉም ከልክ እያለፈ መጣ።
በዚህ ጊዜ አራቱ ቅዱሳን ትልቁንና የመጨረሻውን ውሳኔ አስተላለፉ። ከሰማዕታት ወገን ይቆጠሩ ዘንድ መርጠዋልና ክርስቶስን በሞቱ ይመስሉት ዘንድ ሽተዋልና የሩጫቸው መጨረሻ ሰማዕትነት እንዲሆን መረጡ።
አራቱም ያላቸውን ንብረት ሁሉ ሰብስበው ለነዳያን አካፈሉ። በትከሻቸው ካለች አጽፍ በቀር ስባሪ ገንዘብ ከሃብታቸው አላስቀሩም። ከዚያ ጉዞ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) አደረጉ።
በዙፋኑ የተቀመጠው የመኮንኑ ግርማ መሬት ላይ የፈሰሰው የወገኖቻቸው ደም የሠራዊቱ ድንፋታ ቅዱሳኑን አላስፈራቸውም። በይፋ "ክርስቲያን ነን።" ሲሉ ተናገሩ። በዘመኑ እንዲህ ብሎ መናገር አንገት የሚያስቆርጥ ትልቅ ድፍረት ነበር።
መኮንኑም ከበጐ ሃይማኖታቸው ይለያቸው ዘንድ በእሳት አቃጠላቸው። እግዚአብሔር አዳናቸው። በቀስትም፣ በስለትም፣ በብረትም ለቀናት አሰቃያቸው። ቅዱሳኑ ግን አምላካቸውን አምነው ሁሉን በአኮቴት ተቀበሉ። በመጨረሻ ግን በዚህች ዕለት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ተገድለዋል። ስለ ምጽዋታቸው፣ በጎ አገልግሎታቸውና ሰማዕትነታቸው ጻድቅ፣ ፈራጅ ከሆነ ፈጣሪ አክሊልን ተቀብለዋል።
የበረከት አምላክ ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን።
ሰኔ ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን አበው ሰማዕታት (አባ አክራ፣ አባ ዮሐንስ፣ አባ አብጥልማና አባ ፊልጶስ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯.እናታችን ቅድስት ነሣሒት
"እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና። በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።"
(ዕብ ፮፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ጨምሮ ቅዱስ ላሊበላ፣ ቅድስት አፎምያና ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ ይከበራሉ።
<3 ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት <3
ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር። ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል።
ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል ክብርና ርኅሩኅ የለም። በምልጃውም በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው። መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል። "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል። ቂም የሌለው ለምሕረት የሚፋጠን ደግ መልአክ ነውና።
በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ፣ ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል። እስራኤልን አርባ ዘመን በበርሃ መርቷል፤ መግቧልም። ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል።
(ዘፍ. ፵፰፥፲፮ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ መሳ. ፲፫፥፲፯ ፣ ዳን. ፲፥፳፩ ፤ ፲፪፥፩ መዝ. ፴፫፥፯ ፣ ራእይ. ፲፪፥፯)
ደስ የሚለው ደግሞ ርኅሩኁ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው። ከእናቷ ማኅጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ። ደስ ብሎት ይታዘዛታል። ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ።" ይላታል። ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን በረከትን ያወርዳሉ።
ቅዱስ ሚካኤልን በዚህች ዕለት ስለ እነዚህ ነገሮች እናከብረዋለን።
፩.በመላእክት ሁሉ ላይ አለቃ ሆኖ መሾሙን
፪.ቅዳሴ ቤቱን (ግብጽ ውስጥ)
፫.ቅድስት አፎምያን መርዳቱን
፬.ቅዱስ ባሕራንን መጎብኘቱን
፭.ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማያት ማሳረጉን
፮.ለፍጥረታት ሁሉ ምሕረት የሚጠይቅበት ዕለት ነውና።
ሊቀ መላእክት በክንፈ ረድኤቱ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን።
<3 ቅዱስ ላል ይበላ ንጉሥ <3
በአሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ፦
በብሥራተ መልአክ ተወልዷል።
ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል።
የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት በትሕርምት አድጓል።
በወንድሙ ቢገረፍም ቂም አልነበረውም።
ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል።
በዙፋን ላይ የኢትዮዽያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም እርሱስ አኗኗሩ ገዳማዊ ነበር።
ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር። ለዚያውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት (ጠርዝ) ብቻ ነበር።
በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል።
በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን (ላስታን) ገንብቷል።
ዛሬም ድረስ ምሥጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቃድስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው።
ሥራውን ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል። ጌታችን ስምህን ያከበረ ዝክርህን የዘከረ ከቤትህ ያደረውን ከርስተ መንግሥተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል።
በረከቱን፣ ክብሩን ያድለን።
<3 ቅድስት አፎምያ <3
ከቅዱስ አስተራኒቆስ ጋር በተቀደሰ ትዳር የኖረች፣
ምጽዋትን ያዘወተረች፣
በፍቅረ ቅዱሳን የጸናች፣
ንጽሕናዋን ጠብቃ ሰይጣንን ያሳፈረች ደግ እናት ናት። ዛሬ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ታቅፋ በትእምርተ መስቀልም አማትባ ዐርፋለች። ቅዱሱ መልአክም ወደ ገነት አሳርጓታል።
<3 ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ <3
የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ፣
በሕፃንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ፣
በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ፣
በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ፣
ምጽዋትን ያዘወተረ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው።
በዚህች ቀን ዐርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል።
<3 አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ በረከት ይክፈለን። አሜን። <3
ሰኔ ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፫.ቅድስት አፎምያና ባለቤቷ ቅዱስ አስተራኒቆስ
፬.ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
፭.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ሊቅ
፮.አባ ዮስጦስ ሊቀ ጳጳሳት (የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ደቀ መዝሙር)
፯.አባ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ድሜጥሮስ
፫.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፭.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፮.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
"በሰማይም ሰልፍ ሆነ። ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፤ አልቻላቸውምም። ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ።"
(ራእይ ፲፪፥፯-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ የተድላና የደስታ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
በዚህች ቀን ለአርባ ዓመታት በመላው ዓለም የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት የተከፈቱበት ቀን ይታሠባል።
ይሄስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቡና ታስባ በዓለመ መላእክት ከታየች በኋላ አበው ተስፋ ሲያደርጓት፣
ነቢያት ትንቢት ሲናገሩላት፣
ሱባኤ ሲቆጥሩላት ምሳሌም ሲመስሉላት ኑረዋል።
ዘመኑ በደረሰ ጊዜ በአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጸነሱ ተጸንሳ፣
በመወለዱ ተወልዳ፣
በጥበብና በሞገስ አብራው አድጋ፣
በጥምቀቱ ተጠምቃ፣
በትምህርቱ ጸንታ፣
በደሙ ተቀድሳ፣
በትንሣኤው ከብራ፣
በዕርገቱ ሰማያዊነቷን አጽንታና
በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላት በይፋ ለልጆቿ ተሰጥታለች።
አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በመላው ዓለም ዞረው በብዙ ድካም የሠሯት ቤተ ክርስቲያን ለሁለት መቶ ዓመታት እጅግ የበዙ መከራዎችን አሳልፋለች። በ፪፻፷፭ ዓ.ም የመጣባት መከራ ግን በዓለም ታሪክ እስካሁን አልታየም። የወቅቱ ኃያላን ነገሥታት (ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስ) ዓለምን ለሁለት ተካፍለው ክርስቲያኖችን የማጥፋት ዘመቻ ጀመሩ።
በመጀመሪያም በዓለም ያሉ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እንዲቃጠሉ ካልሆነም እንዲዘጉ በፈንታቸው ደግሞ አጵሎን አርዳሚስ የተባሉ ጣዖቶች እንዲተኩ ትዕዛዝ ተሰጠ። ለአርባ ዓመታት ክርስቲያን ስለሆኑ ብቻ ሚሊየኖች ተገደሉ፤ ታሰሩ፤ ተሰቃዩ፤ ተሰደዱ። መጻሕፍት ተቃጠሉ፤ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ወደሙ።
በአባቶቻችንና እናቶቻችን ላይ ልንናገረው ከምንችለው በላይ ጭንቅና መከራ ደረሰ። ነገር ግን ቅዱሳኑ ያን ሁሉ ችለው ጸኑ። አርባ ሰባት ሚሊየን የሚያህሉትን ደግሞ ሰይፍና እሳት በላቸው። በዛ ዘመን አንድ ቤተ ክርስቲያን ለማግኘት ከአሕጉር አሕጉር መሔድን ይጠይቅ ነበር።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን እግዚአብሔር "ግፍ ይበቃል።" ሲል በ፫፻፭ ዓ.ም ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ነገሠ። መክስምያኖስን በጦርነት ሲማርከው አውሬው ዲዮቅልጢያኖስ ግን አብዶ ሞተ። ይህ ከተደረገ ከዓመታት በኋላ (በ፫፻፲፫ ዓ.ም) ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የዓለም መሪዎችን በዚህች ቀን ጠርቶ አዋጁን በአዋጅ ሻረው። "ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ። በፈንታው ደግሞ ሁሉም ጣዖት ቤቶች ይዘጉ።" አለ።
በሺህ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትን በወርቅ አስለበጠ። በዚህ ምክንያት ይህች ቀን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን "ዕለተ ትፍሥሕት (የደስታ ቀን)" ተብላ ትከበራለች።
ቸሩ አምላክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከመከራ ይሠውርልን። ከበረከቷም ያድለን። ደካሞች ነንና ከማንችለው ፈተናም ይጠብቀን።
ሰኔ ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
፪.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት (ከታላላቆቹ ሶፍያዎች አንዷ)
፬.ቅዱሳት ሰማዕታት ደባሞንና ብስጣሞን (የቅድስት ሶፍያ ልጆች)
፭.ቅዱስ አውሎጊስ ሰማዕት
፮.ቅዱስ ዋርስኖፋ ሰማዕት
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፭.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፮.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
"ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ። ኢየሩሳሌም ሆይ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ። ኢየሩሳሌምስ እርስ በእርሷ እንደ ተገለጠች ከተማ ተሠርታለች።.....
ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም በውስጥሽ ሰላም ይሁን አልሁ።
ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ።"
(መዝ ፻፳፩፥፩-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
በዓሉ ከሠላሳ ሦስቱ ዓበይት የእመቤታችን በዓላት አንዱ ሲሆን በዚህች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል እናቱ እግር ሥር ጠበል አፍልቋል።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን አዝላ ስደት ወጥታ ምድረ ግብጽ ትደርሳለች። በወቅቱ ከደረሱባት ችግሮች አንዱ ደግሞ ረሃብና ጽሙ ነበር። እንኳን ለስደተኛ በቤቱ ላለም ረሃብና ጥም እንዴት እንደሚከብድ የደረሰበት ያውቀዋል።
ለዚያም ነው ሊቁ በቅዳሴው፦
"አዘክሪ ድንግል ረሃበ ወጽምዐ ምንዳቤ ወኀዘነ ወኩሎ ዐጸባ ዘበጽሐኪ ምስሌሁ" ያለው።
ታዲያ አንድ ቀን የበርሃው ፀሐይ አቃጥሏቸው ባረፉበት ድንግል እመቤታችን ውኃ ልመና ወጣች። ብዙ ለመነች ግን ጥርኝ እንኳ የሚሠጣት አጥታ በሐዘን ተመለሰች። ስትመለስ ግን ይባስ ብሎ የልጇን ጫማ ሽፍቶች ወስደውት ደረሰች።
ያን ጊዜ ልጇን ታቅፋ "ውኃ ሳላገኝልህ ጫማህንም አሰረቅኩብህ።" ብላ ምርር ብላ አልቅሳለች።
"በከየት ወትቤ ማርያም ማዕነቅ።
እምሰብአ ሃገር አልቦ ዘየአምራ ለጽድቅ።
ሰአልክዎሙ ማየ ኢወሀሐቡኒ በሕቅ።
ወአሕጎልኩ ለወልድየ አሳእኖ ዘወርቅ።" እንዳለ ደራሲ።
ይህንን የተመለከተ ልጇ የቆመችበትን መሬት ቢባርከው ሕይወትነት ያለው ማይ (ጠበል) ፈለቀ። ጌታችን፣ እመቤታችን፣ ዮሴፍና ሰሎሜ ከውኃው ጠጥተዋል።
ሲሔዱ ግን ለእንግዶች ጣፋጭ (መድኃኒት) ለአካባቢው ሰዎች ግን መራራ ሁኗል።
"ከመ ኢይስተይዋ ሰብአ ሐገር ለይእቲ ማይ አምረራ።
ወለርኁቃንሰ ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ።" እንዳለ መጽሐፍ።
(ሰቆቃወ ድንግል)
ከመቶዎች ዓመታት በኋላም ጌታ ጠበል ያፈለቀበት ድንግል እመቤታችን የቆመችበት ቦታ ላይ በእመ ብርሃን ስም ቤተ ክርስቲያን ታንጿል። ቅዳሴ ቤቱም ተከብሯል። ጠበሉም ሲባርክና ሲፈውስ ይኖራል።
<3 የጠበል በዓል <3
ዳግመኛ ዕለቱ የጠበል በዓል ተብሎም ይታሠባል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለ ጠበል ፈዋሽነት ሁሌ ብታስተምርም በዚህ ቀን ግን ልዩ ትኩረቷ ታደርገዋለች።
እግዚአብሔር በምክንያትም ያለ ምክንያትም መፈወስ ይችላል። ያለ ምክንያት በቃሉና በወዳጆቹ ቃል አድሮ "ዳን" ይላል። ወይም ደግሞ በምክንያት በእመት (እምነት)፣ በጠበል፣ ቅዱስ ቃሉን በመስማት፣ በመስቀሉና በመጻሕፍት በመባረክ (በመታሸት)፣ በቅዱሳን አካል (በልብሳቸው፣ በበትራቸው፣ በጥላቸው፣ በአጽማቸው.....) ይፈውሳል።
እርሱ እግዚአብሔር ነውና በወደደውና በመረጠው አድሮ ያድናል ( ይፈውሳል።)
(፪ነገ. ፭፥፲ ፣ ሐዋ. ፫፥፮ ፤ ፭፥፲፭ ፤ ፲፱፥፲፩)
ዛሬ ግን የጠበል ፈዋሽነት በጉልህ ይነገራል።
(ዮሐ. ፭፥፩ ፤ ፱፥፯)
አምላከ ቅዱሳን ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ በምሕረቱ ይሠውረን። ከድንግል እመቤታችን በረከትም ያሳትፈን።
ሰኔ ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.የእመቤታችን ድንግል ማርያም ቅዳሴ ቤት
፪.የቅዱስ ውኃ (ጠበል) መታሠቢያ
፫.ቅድስት ትምዳ እናታችን
፬.ቅዱስ አውሎጊስ
፭.አባ አትካሮን
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፫.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፬.አቡነ ኪሮስ
፭.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)
"ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። ግርማው በእስራኤል ላይ ኃይሉም በደመናት ላይ ነው።
እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው። የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል። እግዚአብሔርም ይመስገን።"
(መዝ ፷፯፥፴፬-፴፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት አባ ቴዎድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አባ ቴዎድሮስ <3
አባ ቴዎድሮስ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ግብጻዊ አባት ነው። ተወልዶ ባደገባት የእስክንድርያ ከተማ ብሉያትንና ሐዲሳት በወቅቱ ከነበሩ አበው ሊቃውንት ተምሯል። ጊዜው ምንም መናፍቃን የበዙበት ቢሆን በዚያው ልክ እነ ቅዱስ እለ እስክንድሮስና ቅዱስ አትናቴዎስን የመሰሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና ከእነርሱ የሚገባውን ወስዷል።
አባ ቴዎድሮስ "አባ" ያሰኘው ሥራ ገና በወጣትነቱ ድንግልናንና ምንኩስናን በመምረጡ ነበር። ምንም እንኳ ሃብት ከእውቀት ጋር ቢስማማለትም ይህ እርሱን ከምናኔ ሊያስቀረው አልቻለም። ከከተማ ወጥቶ በዓት ወስኖ በጾምና በጸሎት ተወሰነ።
በ፫፻፵ዎቹ ዓ.ም አካባቢ ግን በምዕመናን ላይ ከባድ ችግር ደረሰ። የወቅቱ ነገሥታት በስመ ክርስቲያን አርዮሳውያን ነበሩና ሕዝቡን ማስገደድ አንዳንዴም የአርዮስን እምነት ያልተቀበለውን ማስገደል ጀመሩ። በዚህ ምክንያትም ታላቁ የኦርቶዶክስ ጠበቃ ቅዱስ አትናቴዎስን ከመንበሩ አሳደዱት። በምትኩም አርዮሳዊ ሰው ጳጳስ ተብሎ ተሾመ። ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ እውነተኛ እረኛ ያስፈለገው።
በበዓቱ የነበረው አባ ቴዎድሮስ አላቅማማም። ቤተ ክርስቲያን ትፈልገዋለችና መጻሕፍትን ገልጾ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ምዕመናንን ያጸናቸው ጀመር። መናፍቃኑን ተከራክሮ ምላሽ በማሳጣት ሕዝቡን ከኑፋቄ በመጠበቅ የሠራው ሥራ ሐዋርያዊ ቢያሰኘውም ለአርዮሳዊው ጳጳስ ሊዋጥለት አልቻለም።
በቁጣ ወታደሮችን ልኮ አባ ቴዎድሮስን ተቆጣው። እንዳያስተምርም ገሰጸው። አባ ቴዎድሮስ ግን እሺ ባለማለቱ ግርፋት ታዘዘበት።
ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲገርፉት ረድኤተ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ከዚያ ሁሉ ግርፋት አንዲቷም አካሉ ላይ አላረፈችም። በዚህ የተበሳጨው አርዮሳዊ ጳጳስ የአባ ቴዎድሮስን እጅና እግር ከፈረስ ጋሪ በኋላ አስረው በኮረኮንች መንገድ ላይ በፍጥነት እንዲያሮጧቸው አዘዘ።
ፈረሶቹ መሮጥ ሲጀምሩ የአባ ቴዎድሮስ አካሉ ይላላጥ ጀመር። ትንሽ ቆይቶ ግን እጆቹ ተቆረጡ። በኋላም ራሱ ከአንገቱ ተለይታ መንገድ ላይ ወደቀች። አካሉ በሙሉ መሬት ላይ ተበታተነ። እግዚአብሔር ቅድስት ነፍሱን ተቀብሎ አሳረጋት።
ለቅዱሱም ሦስት አክሊል ከሰማይ ወርዶለታል።
፩.ስለ ፍጹም ምናኔውና ድንግልናው
፪.ስለ ሐዋርያዊ የወንጌል አገልግሎቱ
፫.ስለ ሃይማኖቱ ደሙን አፍስሷልና
"እምአባልከ ተመቲራ ለእንተ ሠረረት ርዕስ
እግዚአብሔር አስተቄጸላ በአክሊል ሠላስ።" እንዳለ መጽሐፍ።
ምዕመናን ሥጋውን ሰብስበው በዝማሬና በማኅሌት በክብር ቀብረውታል።
አምላካችን ከቅዱሱ በረከት ይክፈለን።
ሰኔ ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ቴዎድሮስ ሰማዕት
፪.አባ ገብረ ክርስቶስ
፫.አርባ ሰማዕታት
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል
"መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ። ሩጫውን ጨርሻለሁ። ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ። ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል። ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያሰረክባል። ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።"
(፪ጢሞ ፬፥፯-፰)
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።