gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ፣ ቅዱስ ዋርስኖፋና አባ ዮሐንስ ዘጐንድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ <3

ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በሦስት ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል። እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ ያሉት በሃያዎቹ ውስጥ፣ ቅዱስ ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በሠላሳና በአርባዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን እነ ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ በሃምሳዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ።

ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም፣ ከጐልማሶችም፣ ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው። ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) ስምዖን እና ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል።

ቅዱሱ ጌታችንን ተከትሎ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ፣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ እግር ተምሮ፣ በዕርገቱ ተባርኮ፣ በበዓለ ሃምሳም ሰባ አንድ ልሳናትን ተቀብሎ፣ ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል።

ቅዱስ ታዴዎስ እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል። ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል። ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በኋላም ሐምሌ ፪ ቀን ዐርፏል።

ቅዱሱ ሐዋርያ ያረፈው ሶርያ ውስጥ ሲሆን ከሁለት መቶ ሃምሳ ዓመታት በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ ታንጾለት በዚህች ቀን ወደ ቁስጥንጥንያ ፈልሷል። ይህንን ያደረገው ደግሞ ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ነው። ከሐዋርያው ዘንድም ብዙ ተአምራት ተደርገዋል።

<3 ቅዱስ ዋርስኖፋ ሰማዕት <3

ቅዱሱ በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ገና ከልጅነቱ ጣዕመ ክርስትና የገባው ነበር። መጻሕፍትን በማንበብ ክርስትናንም በመለማመድ ስላደገ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የመወደድ ሞገስ ነበረው። በእድሜው እየጐለመሰ ሲሔድ በተጋድሎውም እየበረታ ሔደ።

በወቅቱ እርሱ የነበረባት ሃገር ጳጳስ በማረፉ ሊቃውንቱና ሕዝቡ ተሰብስበው አምላክን ጠየቁ። እንደሚገባም መከሩ። በደንብ አስተውለዋልና እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሁነው ሁሉም ቅዱስ ዋርስኖፋን መረጡ።

ዛሬን አያድርገውና በአባቶቻችን ዘመን ሕዝቡም ሆነ ሊቃውንቱ መሪ መምረጥን ያውቁ ነበር። ተመራጮቹ ደግሞ እንኳን እንደ ዘመናችን "ሹሙኝ፣ ምረጡኝ" ሊሉ በአካባቢውም አይገኙም ነበር።

ቅዱስ ዋርስኖፋ ለጵጵስና እንደ መረጡት ሲያውቅ "ጐየ" እንዲል መጽሐፍ ጨርቄን ማቄን ሳይል በሌሊት ጠፍቶ በርሃ ገባ። (እንዲህ ነበሩ አበው) በገባበት በርሃ ውስጥ በዓት ሠርቶ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት በርትቶ ዓመታትን አሳለፈ። እርሱ በበርሃ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ጀምሮ ብዙ ክርስቲያኖች አልቀው ነበር።

እርሱ ግን ከዓለም ርቋልና ይህንን አላወቀም ነበር። አንድ ቀን መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ "አንተ በስሙ ደማቸውን ለሚያፈሱ አክሊላት እየታደለ ሰማያዊ ርስትም እየተካፈለ ነውኮ! አልሰማህም?" አለው።

ቅዱስ ዋርስኖፋም "ለካም እንዲህ ያለ ክብር አምልጦኛል።" ብሎ በርሃውን ትቶ ወደ ከተማ ወጣ። መልአኩ እንዳለውም ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ደረሰ። ቅዱሱም ሳያመነታ ስመ ክርስቶስን ሰብኮ ብዙ ተሰቃይቶ በዚህች ቀን አክሊለ ሰማዕትን በአክሊለ ጻድቃን ላይ ደርቧል።

<3 እጨጌ አባ ዮሐንስ ዘጐንድ <3

ጻድቁ ተወልደው ያደጉት በኢየሩሳሌም ሲሆን ነገዳቸውም እስራኤላዊ ነው። ነገር ግን ተጋድሏቸውን የፈጸሙት በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እጨጌ አባ ዮሐንስ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቀጥሎ ባለ ረዥም እድሜ ጻድቅ መሆናቸው ይነገራል።

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያረፉት በአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታቸው ሲሆን እጨጌ አባ ዮሐንስ ደግሞ በአምስት መቶ ዓመታቸው ነው:: የሚገርመው ጻድቁ የታላላቁ ጻድቃን ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ተክለ ሃይማኖት፣ ሳሙኤል፣ ዜና ማርቆስና ሌሎችም ባልንጀራ ነበሩ።
እጨጌ አባ ዮሐንስ በሃገራችን አምስት በዓቶች የነበሯቸው ሲሆን በአንድ በዓት የሚኖሩት ለሃምሳ ዓመታት ነበር።

በዚህም በኢየሩሳሌም ለሃምሳ ዓመታት በኢትዮጵያ ደግሞ ለአራት መቶ ሃምሳ ዓመታት ኑረዋል። ከበዓቶቻቸው አንዱ ደብረ ሊባኖስ ሲሆን በገዳሙ ለሃምሳ ዓመታት አበ ምኔት (እጨጌ) ሆነው አገልግለዋል። "እጨጌ" የሚባሉትም በዚህ ምክንያት ነው።

ጻድቁ የመጨረሻ ዘመናቸውን ያሳለፉት በጐንድ (ጉንድ) ተክለ ሃይማኖት ገዳም ነው። ገዳሙ የሚገኘው በሰሜን ጐንደር ዞን በለሳ ወረዳ ውስጥ ሲሆን የመሠረቱትም ራሳቸው ናቸው። ነገር ግን በራሳቸው እንዲጠራ አልፈለጉምና ገዳሙ የሚጠራው በወዳጃቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም ነው።

ጐንድ እኛ ኃጥአን ሳይገባን ያየነው ገዳም ነው። ዛሬም ድረስ ድንቅ የሆኑ አበው የሚኖሩበት፣ ተአምራትም የማይቋረጥበት፣ ፈዋሽ ጠበል ያለው ደግ ገዳም ነው። ጻድቁ እጨጌ አባ ዮሐንስ ግን አስታዋሽ አጥተው እየተዘነጉ ካሉ ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ምንም ዛሬ አጽማቸው ፈልሶ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ቢሔድም እርሳቸው በአምስት መቶ ዓመታቸው ያረፉት በዚህ ገዳም ውስጥ ነው።

እግዚአብሔር ከሐዋርያው፣ ከሰማዕቱና ከጻድቁ ክብርን በረከትን ያሳትፈን።

ሐምሌ ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
፪.ቅዱስ ዋርስኖፋ ሰማዕት
፫.እጨጌ አባ ዮሐንስ (ዘጐንድ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪.ቅድስት አርሴማ ድንግል
፫.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፭.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊት
፮.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)

"ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ። የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም ጐበዞች ሆይ! ለሽማግሌዎች ተገዙ። ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና። ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።"
(፩ጴጥ ፭፥፫-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአበው ቅዱሳን ሴት፣ ሕዝቅኤል ነቢይ እና ዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ሴት ነቢይ <3

አባታችን ሴት የመጀመሪያዎቹ ፍጥረቶች የአዳምና ሔዋን የተባረከ ልጅ ነው። ቀደምተ ፍጥረት አዳም እና ሔዋን በዕጸ በለስ ምክንያት ከገነት ከተባረሩ በኋላ በመጀመሪያ ቃየን እና አቤልን ከነ መንትያዎቻቸው ወልደው ነበር።

ነገር ግን የልጅ ደስታቸው ቀጣይ ሊሆን አልቻለም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቃየን ሲሆን ወንድሙን አቤልን በጾታዊ ፍላጐት ምክንያት በመግደሉ ነበር። የአቤል ሞት ለአባታችን አዳም መራር ዜና ነበር። ወላጅ እንኳን ደጉን ይቅርና ክፉ ልጁም እንዲለየው አይፈልግምና።

ቅዱስ አዳም ቅዱስ አቤልን ቀብሮ ፈጽሞ አለቀሰ። ልቅሶውም እንዲሁ የወርና የሁለት ወር አልነበረም። አራት ኢዮቤልዩ (ሃያ ስምንት ዓመታት) ነበር እንጂ። ይህንን ሐዘንና ልቅሶ የተመለከተ እግዚአብሔር ደግሞ ደግ ፍሬን በሔዋን ማኅጸን ውስጥ አሳደረ።

ይህ ሕፃን በተወለደ ጊዜ "ሴት" ብለው ስም አወጡለት። ትርጉሙም "የአቤል ምትክ" እንደ ማለት ነው። ሴት ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በብዙ ነገሩ አዳምን የሚመስል ነበረ። ደም ግባቱ፣ ቅንነቱ፣ ታዛዥነቱ፣ ደግነቱ ሁሉ ልዩ ነበር። በዚህም አዳምና ሔዋን ተጸናንተዋል።

ትልቁ ነገር ደግሞ ዓለም የሚድንባት እመቤት ድንግል ማርያም ከስልሳ በላይ የአዳም ልጆች ተመርጣ ለቅዱስ ሴት መሰጠቷ ነው። ይህንን ምሥጢርና የሴትን ማንነት ያስተዋለው ሊቁ አባ ሕርያቆስ እመ ብርሃንን እንዲህ ሲልም አመስግኗታል።
"ሒሩቱ ለሴት - የሴት ደግነቱ፣ በጐነቱ፣ ቅንነቱ አንቺ ነሽ።"
(ቅዳሴ ማርያም)

አባታችን ሴት በሚገባው ትዳር ተወስኖ ቅዱስ ሔኖስንና ሌሎች ብዙ ልጆችን ወልዷል።

አባታችን አዳም ባረፈ ጊዜ የዚህን ዓለም እረኝነት (በደብር ቅዱስ ላሉት) ተረክቧል። አዳምም ልጆቹንና ወርቅ እጣን ከርቤውን አስረክቦታል። ሴት እንባው እንደ ዥረት እየፈሰሰ አስቀድሞ አዳምን አስከትሎም ሔዋንን ገንዞ በክብር ቀብሯቸዋል።

ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤውን ከሥጋቸው ጋራ በቤተ መዛግብት (በተቀደሰው ዋሻ) ውስጥ አኑሮታል። የአገልግሎት ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ ደጉ ሴት ኃላፊነቱን ለልጁ ሔኖስ ሰጥቶ በዘጠኝ መቶ አሥራ ሁለት ዓመቱ ዐርፏል። እርሱም ከወላጆቹ አዳምና ሔዋን ጋር ተቀላቅሏል።

<3 ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ <3

ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል የነበረው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በአምስት መቶ ዓመት አካባቢ ሲሆን የጼዋዌ (ምርኮ) አባልም ነበር። እስራኤልና ይሁዳ ወደ ባቢሎን በምርኮ ሲወርዱ አብሮ ወርዷል። ቅዱሱ ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ሐረገ ትንቢቱም በአርባ ስምንት ምዕራፎች የተዋቀረ ነው።

በዘመኑ ሁሉ ቅድስናን ያዘወተረው ቅዱሱ ከደግነቱ የተነሳ በጸጋማይ (ግራ) ጐኑ ተኝቶ ቢጸልይ ስድስት መቶ ሙታንን አስነስቷል። ወገኖቹ እስራኤልንም ያለ መታከት አስተምሯል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት ታላቁን ራእይ እንዳየ ታስተምራለች። ነቢዩ በፈለገ ኮቦር ካያቸው ምሥጢራት እነዚህን ያነሷል።
፩.እግዚአብሔርን በዘባነ ኪሩብ ተቀምጦ ሲሠለስና ሲቀደስ አይቶታል። የኪሩቤልንም ገጸ መልክእ በጉልህ ተመልክቷል።
(ሕዝ. ፩፥፩)

፪.በመጨረሻው ቀን ትንሣኤ ሙታን ትንሣኤ ዘጉባኤ እንደሚደረግም ተመልክቷል።
(ሕዝ. ፴፩፥፩)

፫.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ኆኅት ኅትምት/ኆኅተ ምሥራቅ (የምሥራቅ ደጅ) ሁና አይቷታል።

ይህ የምሥራቅ ደጅ (በር) ለዘላለም እንደታተመ ይኖራል። የኃያላን ጌታ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ወጥቷልና።
(ሕዝ. ፵፬፥፩)
በመጨረሻ ሕይወቱ እስራኤል ለክፋት አይቦዝኑምና ነቢዩን አሰቃይተው ገድለውታል።

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ <3

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግሥተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው።

ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስ እና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ በገሊላ አካባቢ አድጐ ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል። ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር። ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕፃን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው።

ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል። ከእርሷ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ። ስንኳን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላእክትም ማዕረጉ ከፍ አለ። ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል። ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል። ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው።

በዚህ ቀንም ቅዱስ ዮሐንስ በታናሽ እስያ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መስበኩ ይታሰባል። ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ለሰባ ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው። ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል።

ሦስት መልእክታት፣ ራእዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል። ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል። ከእሳት እስከ ስለት እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል። እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጓቸዋል። ዳግመኛ ይህች ዕለት ለሐዋርያው ቅዳሴ ቤቱ ናት።

እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲህ ነው።
ወንጌላዊ
ሐዋርያ
ሰማዕት ዘእንበለ ደም
አቡቀለምሲስ(ምሥጢራትን ያየ)
ታኦሎጐስ (ነባቤ መለኮት)
ወልደ ነጐድጓድ
ደቀ መለኮት ወምሥጢር
ፍቁረ እግዚእ
ርዕሰ ደናግል (የደናግል አለቃ)
ቁጹረ ገጽ
ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ (ከጌታ ጎን የሚቀመጥ)
ንስር ሠራሪ
ልዑለ ስብከት
ምድራዊው መልዐክ
ዓምደ ብርሐን
ሐዋርያ ትንቢት
ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
ኮከበ ከዋክብት

በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር። የሴት ደግነቱ የሕዝቅኤልም በረከቱ ይደርብን።

ሐምሌ ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሴት ነቢይ (ወልደ አዳም)
፪.ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ
፫.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ቅዳሴ ቤቱ)
፬.ቅዱስ አሞን ሰማዕት
፭.ቅድስት መስቀል ክብራ

ወርኀዊ በዓላት
፩.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪.አቡነ መብዐ ጽዮን ጻድቅ
፫.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፮.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

"..... "እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም።" ይላል ጌታ እግዚአብሔር። "የእስራኤል ቤት ሆይ! ተመለሱ። ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ። ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?" በላቸው።"
(ሕዝ ፴፫፥፲፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ መርቆሬዎስ እና ለቅዱሳኑ ቴክላ፣ አበከረዙን፣ ዱማድዮስ እና ሄኖክ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕተ ሮሜ <3

ቅዱሱ ከቀደምት ሰማዕታት አንዱ ሲሆን በ፪፻ ዓ.ም አካባቢ እንደ ተወለደ ይታመናል። ወላጆቹ ከጣዖት አምልኮ ወደ ክርስትና የመጡት በተአምር ነው። ስማቸውም ታቦት እና ኖኅ ይባላሉ። ቅዱሱ መጀመሪያ "ፒሉፓዴር" ይባል ነበር። ትርጉሙ "የአብ ወዳጅ" እንደ ማለት ነው።

ቀጥሎም "መርቆሬዎስ" ተብሏል። ይኸውም "የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው። በጦርነት ኃይለኛ፣ በመልኩ ደመ ግቡና ተወዳጅ የነበረው ቅዱስ መርቆሬዎስ ስለ ክርስትናው መከራን የተቀበለው በሃያ ዓመቱ ነው። ዘመኑም በዳኬዎስ ቀዳማዊ ነው።

ስለ ሃይማኖቱም ለአምስት ዓመታት መከራን ታግሦ በሃያ አምስት ዓመቱ ማለትም በ፪፻፳፭ ዓ.ም ኅዳር ፳፭ ቀን አንገቱን ተከልሏል። በዓለማቀፍ ደረጃም ቅዱስ መርቆሬዎስ ክብሩ ከሊቀ ሰማዕታት ቀጥሎ የሚገኝ ነው።

በተለይ ዛሬ ሐምሌ ፳፭ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ሲሆን ቤቱ በታነጸበት ሁሉ ተአምራትን ያደርጋል። ስለዚህ ነገር ታሪክ ብቻ ሳይሆን እኛ ኃጥአንም ምስክሮች ነን። ጋሹ አምባን ጨምሮ ዛሬም ቅዱሱ ድንቆችን ይሠራል።

<3 ቅዱስ ሄኖክ ነቢይ <3

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ሄኖክ ከአባታችን አዳም ሰባተኛው ደግ ሰው ሲሆን አባቱ ያሬድ ይባላል። በእርግጥ ቅዱሱ ሚስት አግብቶ ማቱሳላ እና ሌሎች ልጆችን ወልዷል። አካሔዱ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ነበርና ሞትን አላየም።

ነቢዩ ሄኖክ በ፲፬፻፹፮ ዓ.ዓ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (መጽሐፈ ሄኖክን) ጽፏል። የዚህ መጽሐፍ ባለቤት ደግሞ ሃገራችን ናት። ቅዱሱ ብዙ ሰማያዊ ምሥጢሮችን ተመልክቷል።

የእርሱ ሞትን አለመቅመስ በአቤል ሞት የፈሩትን ውሉደ አዳም በተስፋ አነቃቅቷቸዋል።
"በአቤል አፍርሆሙ
ወበሄኖክ አንቅሆሙ።" እንዳለው ሊቁ።
(ዘፍ. ፭፥፳፬ ፣ ሄኖክ. ፬፥፩)

<3 ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት <3

እናታችን ቅድስት ቴክላ በኒቆምድያ ተወልዳ ያደገች ከአሕዛባዊ እምነት ወደ ክርስትና በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አማካኝነት የመጣች እናት ናት። እርሷ ክርስትናን ከልብ ለሚሹ ሴቶች ሁሉ መሪና ትልቅ ት/ቤት ናት። ወንጌልን ከሐዋርያው ስትማር ምሥጢሩ እየመሰጣት አንዳንዴ ለሦስት ቀናት ምግብ አትቀምስም ነበር።

እጅግ ቆንጆ፣ ወጣትና የሃብታሞች ልጅ ብትሆንም ስለ ክርስቶስ ሁሉን ለመናቅና መስቀሉን ለመሸከም አልተቸገረችም። ከኒቆምድያ እስከ አንጾኪያ ወንጌልን ሰብካለች። ወላጆቿን ጨምሮ ብዙ ነፍሳትን አድናለች። በፈንታውም ብዙ መከራን ተቀብላ በዚህች ቀን ዐርፋለች። ቤተ ክርስቲያን "ሐዋርያዊት" ብላ ታከብራታለች።

<3 ቅዱስ አበከረዙን ጻድቅ ወሰማዕት <3

ስም አጠራሩ የከበረ ታላቁ አባ አበከረዙን ወደ ክርስትና የተጠራው ከሽፍታነት (ስርቆት) ሕይወት ነው። ከአጋሮቹ ጋር ገዳም ለመዝረፍ ሒደው አንድ ባሕታዊ ከማታ አሥራ ሁለት ሰዓት እስከ ጧት አሥራ ሁለት ሰዓት ሲጸልይ አይተው ተጸጽተው ንስሐ ገብተዋል።

አበከረዙን ግን ዓለምን ንቆ በምናኔ ለሰባት ዓመታት ተጋድሏል። ነገር ግን ሰማዕት ለመሆን ከነበረው ፍቅር የተነሳ ከገዳም ወደ ከሃድያን ነገሥታት ሃገር ሔዶ ስመ ክርስቶስን ሰብኳል። በእርሱ ላይ ከደረሱ ስቃዮች ብዛት የተነሳ ከሥጋው፣ ከአጥንቱና ከደሙ የተረፈለት የለም።

እንዲያውም አንዴ በዓየር ላይ ዘቅዝቀው ሰቅለው ደሙ በአፍና በአፍንጫው እየጐረፈ ለአሥር ቀናት ቆይቷል።
በወቅቱ የመኮንኑ ሴት ልጅ እየመጣች ያለ ርኅራኄ ታሰቃየው ነበርና እርሷን መልአክ ወርዶ ቀሥፎ ገደላት።

እርሱ በተሰቀለ በሃያ ሁለተኛው ቀን እርሷ በተቀበረች ደግሞ በአሥራ ሁለተኛው ቀን ከተሰቀለበት አውርደውት ከሞት አስነስቷታል። ታላቁ አበከረዙንን በዚህች ቀን ብዙ አሰቃይተው፣ ወገቡን ሰብረው፣ አንገቱንም ሰይፈው ገድለውታል።

<3 ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ <3

ለቤተ ክርስቲያን በንጹሕ ሕይወታቸው ካበሩላት ዐበይት ቅዱሳን አንዱ ቅዱስ ዱማድዮስ ነው። እርሱ ወደ ክርስትና የመጣው ከባዕድ አምልኮ ሲሆን መሪው መንፈስ ቅዱስ ነው። ጣዕመ ሕይወቱን ሲሰሙት ዕዝነ ልቡናን ደስ ያሰኛል።

ገና በወጣትነቱ እንደ ሐዋርያት ሰብኮ አሕዛብን አሳምኗል። እንደ ጻድቃን አካሉ አልቆ አጥንቶቹ እስኪታዩ ተጋድሏል። እርሱ ድንግል፣ ንጹሕ፣ መነኮስ፣ ባሕታዊና ካህን ነው። ግን ውዳሴ ከንቱን አምርሮ ይጠላል። በዚህ ምክንያት ካደረበት አይውልም ከዋለበትም አያድርም።

እርሱ በጸሎቱ የተዘጉ ማኅጸኖችን ከፍቷል። ዕውራንን አብርቷል፣ ለምጻሞችን አንጽቷል፣ አንካሶችን አርትቷል፣ በፈጣሪው ኃይል ፈሳሽ ወንዝን አቁሟል። እንደ ገናም እንደ ነበረው መልሶታል።

የቅዱስ ዱማድዮስ መጨረሻው ደግሞ ሰማዕትነት ነው። በበዓቱ ውስጥ ሳለ ከደቀ መዝሙሩ ጋር ክፉዎች በድንጋይ ወግረው ገድለውታል። ድንጋዩም የኮረብታ ያህል ነበር። ልክ በዓመቱ በዚህች ዕለት ምዕመናን ሥጋውን አፍልሠዋል።

ቸር አምላክ ከነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ክብርን ያሳትፈን።

ሐምሌ ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
፪.ቅዱስ ሄኖክ ነቢይ (ዕርገቱ)
፫.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፬.ቅዱስ አበከረዙን ታላቁ (ጻድቅና ሰማዕት)
፭.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ (ጻድቅና ሰማዕት)
፮.ቅድስት ኢላርያ ሰማዕት
፯.ቅዱሳት ቴክላ ወሙጊ ሰማዕታት
፰.ቅዱስ እንዲኒና ሰማዕት
፱.አባ ይስሐቅ ሰማዕት
፲.አባ ሕፃን ሞዐ ዘደብረ ሊባኖስ
፲፩.ሃያ አምስት ሺህ ሰማዕታት (የአትሪብ - ግብጽ ሰዎች)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
፪.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፫.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

"እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና። በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።"
(ዕብ ፮፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ጊዮርጊስ ኃያል አስተበቁዓከ፡፡
ከመ ታድኅነኒ እግዚእየ ለእሩቅ ገብርከ፡፡
አልባሰ ዚአከ በደመ በግዕ ዘኀፀብከ፡፡
ወእምሰረቀት ፍጹመ ዐቀብከ፡፡"

(ኃያሉ ሰማዕት ሆይ እኔን ምስኪኑን አገልጋይህን ከሃይማኖት መራቆት ከምግባር እጦት ታድነኝ ዘንድ እማልድሃለሁ፡፡
ልብሰ ተጋድሎህን በበጉ በክርስቶስ አጥበህ ከአላውያን ቀማኞች ከከሐድያን ወንበዴዎች ጠብቀህ ክብረ ልብስህን በክብር ለመልበስ በቅተሃልና፡፡)
(መልክአ ጊዮርጊስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ።"
(ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱስ ዑራኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ድንግል እመቤታችንና ቅዱስ ዑራኤል <3

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዚህች ቀን ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል፦
፩.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጓታል። በሠረገላ ብርሃን ጭኖ በክንፎቹም ተሸክሞ አስቀድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል። በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ፣ የምትለምንና የምትማልድ ሆናለች። ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች።
፪.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መርቶ አምጥቷታል። በክንፉ ተሸክሞ በአራቱም አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጓል።
፫.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ አፍስሷል።
፬.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል።

<3 አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ኢትዮጵያዊ <3

ወላጆቻቸው ማርቆስ እና እግዚእ ክብራ ይባላሉ። ተአምራትን ገና ከእናታቸው ማኅጸን ጀምሮ ይሠሩ የነበሩት ጻድቁ በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው መንነዋል። በስብከተ ወንጌልም ትግራይና አካባቢውን አድርሰዋል። በእነዚህም ጊዜያት ብዙ አርድእትን አፍርተዋል።

በጋሥጫ ገዳም መስርተው የወንድና የሴት ብለውም ለይተዋል። ሲጸልዩም ሆነ ሲያስተምሩ ተደሞ ይመጣባቸው የነበረ ሲሆን አንድ ቀን እባቡን ዓሣ አድርገው ደቀ መዛሙርትን አስደንቀዋል።

ከጾም፣ ከጸሎትና ከስግደት ባሻገር ከወቅቱ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን መከራ በመቀበላቸው እንደ ሰማዕትም ይቆጠራሉ። ከብዙ የገድል ዓመታት በኋላም በ፲፫፻፴ ዓ.ም በዚህች ቀን ትግራይ ውስጥ ዐርፈዋል። በቆይታ ግን ወደ ጋሥጫ ዐጽማቸው ፈልሷል።

<3 ቅዱስ ላዕከ ማርያም ኢትዮጵያዊ <3

ቅዱሱ የአፄ ናዖድ የልጅ ልጅ፣ የቅድስት ሮማነ ወርቅ ልጅ፣ የልብነ ድንግል የእኅት ልጅና የገላውዴዎስ አጐት ነው። በግራኝ አህመድ ዘመን ተማርኮ ወደ የመን ከዚያም ቱርክ ተወስዷል።

ሃይማኖቴን አልክድም ስላለ ብዙ አሰቃይተው አባለ ዘሩን ቆርጠው ጃንደረባ አደረጉት። በድንቅ ተአምር ግን ወደ ሃገሩ ተመለሰ። እስከ ዕለተ ሞቱም ነዳያንን ሲያበላ ኑሮ ዛሬ ዐርፏል።

<3 ቅዱስ ሱስንዮስ <3

በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ የኤፌሶን ሰው ሲሆን ጃንደረባም ነበር። በ፬፻፴፩ ዓ.ም ሁለት መቶውን የጉባዔ ኤፌሶን ሊቃውንት አገልግሎ በዚያው ዓመት ዐርፏል። ቅዱስ ቄርሎስ ገንዞ ቀብሮታል።

<3 ብፁዕ አወ ክርስቶስ <3

ከተባረከች ሚስቱ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ግን ደግሞ በድንግልና ኑረዋል። ቀን ቀን እንግዳ ሲቀበሉ ነዳያንን ሲያበሉ ውለው ሌሊት ሲገሰግዱና ሲጸልዩ ያድሩ ነበር። ጌታችን ከሰማይ መስክሮላቸው ዛሬ ዐርፈዋል።

<3 ቅዱስ ዮራኖስ <3

በሉቃስ ወንጌል ላይ (ሉቃ. ፳፫፥፵፯) የምናገኘው የመቶ አለቃው ሲሆን በጌታችን ትንሣኤ ቀን የጠፋች ዓይኑ በርታለት በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት በቅቷል።

ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟን ፍቅሯን ከቅዱሳኑ ሁሉ ጸጋ በረከትን እግዚአብሔር ያድለን።

ሐምሌ ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
፪.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፫.አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
፬.ቅዱስ ላዕከ ማርያም ሔር (ኢትዮጵያዊ)
፭.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ኢትዮጵያዊ) ልደታቸው
፮.ብፁዕ አወ ክርስቶስና ሚስቱ (ጻድቃን)
፯.ቅዱስ ሱስንዮስ ጻድቅ
፰.ቅዱስ ዮራኖስ መኮንን (የመቶ አለቃው)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አበው ጎርጎርዮሳት
፪.አቡነ ምዕመነ ድንግል
፫.አቡነ አምደ ሥላሴ
፬.አባ አሮን ሶርያዊ
፭.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

"እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ። ጽድቅንም አደረጉ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፪-፴፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"እግዚአብሔር ሤመ ረድኤቶ ለንእስናከ ዐቃቤ
ወስምዖ መጥበቤ
ፍትወ ምግባር ቂርቆስ ወምዑዘ ኂሩት እምከርቤ
ለዘተጽዕረ በምንዳቤ ወለዘቈስለ በጥብጣቤ
ለአባልከ ሰላም እቤ።"

(እግዚአብሔር ረድኤቱን ለታናሽነትህ ጠባቂን አስቀመጠ፤ ብልኅ የሚያደርግ ምስክርነቱንም፤ ምግባርህ ያማረ በጎነትህ ከከርቤ ይልቅ የሚሸት ቂርቆስ፤ በመከራ የተቸገረ በግርፊያ የቆሰለ ለሆነ ሰውነትህ ሰላም እላለሁ።)
(ሊቁ አርከ ሥሉስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ <3

ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል ትልቅ ሞገስ የነበረውና "የጌታችን ወንድም" ተብሎ የተጠራ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ የሞተችው እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች። በቤት ውስጥም ስምዖን፣ ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ የምትባል እኅትም ነበረችው።

እናቱ ማርያም ከሞተች በኋላ ዕጓለ ማውታ (ድሃ አደግ) ሆኖ ነበር። ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ ቤተሰብ ተቀየረ። የበረከት፣ የምሕረትና የሰላም እመቤት የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው።

እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ አለቀሰች። የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው ቆሽሸው ነበር። በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ ያሳዝን ነበር። እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም። ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውኃ አምጥታ የሕፃኑን ገላ አጠበችው። (በአምላክ እናት የታጠበ ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል።)

እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ከተወለደ በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ሕፃኑን ያዕቆብን ተንከባከበችው። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ግን ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ። ከስደት መልስ ግን ለሃያ አምስት ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ ትዝ ብላው አታውቅም። አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና።

ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና ወተትን) ብቻ ነው። ስለዚህም፦
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል መጽሐፍ።
(መልክዐ ስዕል)

ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል።
ለዚህም ምክንያቱ
፩.ለሠላሳ ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፣
፪.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእኅት ልጅ በመሆኑ፣
፫.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች በመሆናቸው፣
፬.ጌታችን ከትኅትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን "ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው። (ሥጋቸውን ተዋሕዶ ተገኝቷልና።)

ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ።" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ገልጧል።
(ያዕ. ፩፥፩)
ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው።
ከሰባ ሁለቱ አርድእት ተቆጠረ።
ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም።" ብሎ ማክፈልን አስተማረ።
መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ።
የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ አገለገለ።
በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ።
ሙታንን አስንስቶ፣ ድውያንን ፈውሶ፣ የመካኖችን ማኅጸን ከፍቶ፣ አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተአምራትን ሠራ። እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ መልካሙን ገድል ተጋደለ።

በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ ነው?" ሲሉ ጠየቁት። እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው፤ የእኔም ወንድሜ ነው።" እንዲላቸው ጠብቀው ነበር። (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት)

በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ። "ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦
አምላክ፣
ወልደ አምላክ፣
ወልደ አብ፣
ወልደ ማርያም፣
ሥግው ቃል፣ እግዚአብሔር ነው። እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት ወንድሙ አይደለሁም።" አላቸው።

ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት። በገድል የተቀጠቀጠ አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት። አንዱ ግን ከእንጨት የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ መታው። ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ። ሰማዕቱ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ።

ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር። በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ፣ ጸጉሩን ተላጭቶ፣ ገላውን ታጥቦና ልብሱን ቀይሮ አያውቅም።
"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ" እንዲል።

ከጾም፣ ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ አላራምድህ ብሎት ነበር። ስለዚህም አበው "ጻድቁ (ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል።
ቅዱሱ ሐዋርያ "የያዕቆብ መልእክት" የሚለውን ባለ አምስት ምዕራፍ መልእክት ጽፏል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን። በምልጃውም ምሕረትን ይላክልን።

ሐምሌ ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት)
፪.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስ ሰማዕት
፬.ዘጠኝ ሺህ ሰማዕታት (የቅዱስ ኤስድሮስ ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
፫.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

"የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት። ትዕግስትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።"
(ያዕ ፩፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ) <3

ቅዱሱ "ወንጌሉ ዘወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ከሌሎች ዮሐንስ ከሚባሉ ቅዱሳን ለመለየት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን እድሜ ልኩን የሚያነበው፣ ከእጁ የማይለየውና አቅፎት የሚተኛ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል ስለ ነበረው ነው።

የቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩ ከመርዓዊ (ሙሽራው) ገብረ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ሙሴ ሮማዊ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በሮም ግዛት ሥር የሚኖሩ አጥራብዮስና ብዱራ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ። እግዚአብሔር በቀደሰው ትዳር የሚኖሩና ነዳያንን የሚዘከሩ ነበሩና ይህንን ቅዱስ ወለዱ። ስሙን ዮሐንስ ብለው እንደሚገባም አሳድገው ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያትን እንዲረዳ ለመምህር ሰጡት። ቅዱስ ዮሐንስ ከመምህሩ ዘንድ ቁጭ ብሎ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን ተማረ።

ለወላጆቹ ቅንና ታዛዥ ነበርና አባቱ "ልጄ! የምትፈልገውን ጠይቀኝ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለው። ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድሮ እኛን የሚያምረን ሁሉ አላሰኘውም። አባቱን "ቅዱስ ወንጌልን ግዛልኝ፤ በወርቅም አስለብጠው።" አለው። አባትም የተባለውን ፈጸመ።

ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እስካረፈባት ቀን ድረስ ቅዱስ ዮሐንስና የወርቅ ወንጌሉ ተለያይተው አያውቁም። ሁሌም ያለመታከት ያነበዋል። ሲቀመጥም፣ ሲነሳም፣ ሲሔድም፣ ሲተኛም አብሮት ነበር።

ቅዱስ ዮሐንስ ወጣት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይድሩት ዘንድ ተዘጋጁ። ልብሰ መርዐም (የሙሽራ ልብስ) አዘጋጁ። በዚያው ሰሞን ግን አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤታቸው መጥቶ ያድራል። በዚያች ሌሊት መነኮሱ በጨዋታ መካከል ስለ ቅዱሳን መነኮሳት ተጋድሎና ክብር ነገረው። የሰማው ነገር ልቡናውን የማረከው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደ ፈጣሪው ይለምን ነበር።

አንድ ቀን ግን ያ መነኮስ በድጋሚ መጥቶ አደረ። ቅዱስ ዮሐንስ መነኮሱን ወደ ገዳም እንዲወስደው ቢጠይቀው "አይሆንም አባትህ ያዝንብኛል።" አለው። ቅዱሱ ግን "በእግዚአብሔር ስም አማጽኜሃለሁ።" ስላለው ሁለቱም በሌሊት ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ።

አበ ምኔቱ "ልጄ! የበርሃውን መከራ አትችለውም ይቅርብህ።" ቢለውም "አባቴ! አይድከሙ ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር አይለየኝም።'' ስላላቸው እንደሚገባ ፈትነው አመንኩሰውታል። ቅዱስ ዮሐንስ ከመነኮሰ በኋላ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና በትሕርምት ያሳየው ተጋድሎ በርካቶችን አስደነቀ።

ለሥጋው ቦታ አልሰጣትምና በወጣትነቱ አካሉ ረገፈ። ቆዳውና አካሉም ተገናኘ። ሥጋውን አድርቆ ነፍሱን አለመለማት። በእንዲህ ያለ ሕይወት ለሰባት ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በራእይ "ወደ ወላጆችህ ተመለስ።" እያለ ሦስት ጊዜ አናገረው።
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ አበ ምኔቱ ሒዶ ቢጠይቀው "ራእዩ ከእግዚአብሔር ነው።" ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አሰናበተው።

ቅዱስ ዮሐንስ በላዩ ላይ የነበረችውን ልብስ በመንገድ ለነዳይ ሰጥቶ በፈንታው ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ ከወላጆቹ በር ላይ ለመነ። "እባካችሁ አስጠጉኝ።" አላቸው። ወላጆቹ በጭራሽ ሊለዩት አልቻሉም። ነገር ግን አሳዝኗቸዋልና በበራቸው አካባቢ ትንሽ ቤት ሠሩለት።

በዚያች በዓት ውስጥ እንዳስለመደ በትጋት ለሰባት ዓመታት ተጋደለ። በእነዚህ ዓመታት እንኳን ሌላው ሰው ወላጆቹም ቢሆኑ ፍርፋሪ ከመስጠት በቀር አይቀርቡትም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ "ይሸተናል" የሚል ነበር። በመጨረሻም መልአከ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ "ከሰባት ቀናት በኋላ ታርፋለህ።" አለው።

እናቱን ጠርቶ "አንድ ነገር ልለምንሽ።" አላት:: "እሺ" አለችው። "ከሞትኩ በኋላ በለበስኳት ጨርቅ እንድትገንዙኝ በበዓቴ ውስጥም እንድትቀብሩኝ።" አላትና የወርቅ ወንጌሉን አውጥቶ ሰጣት። ያን ጊዜ አባቱም ደርሶ ነበርና ደነገጡ።

የወርቅ ወንጌሉን ለዩት። ልጃቸውን ግን መለየት አልቻሉምና እያለቀሱ ስለ ልጃቸው የሚያውቀው ካለ እንዲነግራቸው ለመኑት። እርሱም "ልጃችሁ ዮሐንስ እኔ ነኝ።" አላቸው።

በዚያች ቅጽበት ወላጆቹ የሰሙትን ማመን አልቻሉም። በፍጹም ዋይታ እየጮሁ አለቀሱ። ለቅሷቸውን የሰሙ ሁሉ ተሰበሰቡ። ለሰባት ቀናት እኩሉ እያለቀሰ እኩሉ እየተባረከ በዓቱን ከበው ሰነበቱ። በሰባተኛው ቀን መልአኩ መጥቶ በክብር ነፍሱን ተቀበለ።

እናቱ የልጇን አደራ ረስታ (እርሷስ መልካም አደረግሁ ብላ ነው።) ለሠርጉ ባዘጋጀችው የወርቅ ልብስ ገነዘችው። ወዲያው ግን በጽኑ ታመመች። አባት ግን ፈጠን ብሎ በዚያች ጨርቅ ገንዞ በበዓቱ ውስጥ ቀበረው። ያን ጊዜ እናት ፈጥና ዳነች። ከቅዱሱ መቃብርም ብዙ ተአምራትና ፈውስ ተደርጓል።

ቸሩ አምላካችን ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ጸጋ በረከትን ይክፈለን።

ሐምሌ ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
፬.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮.አባ ዳንኤል ጻድቅ

"እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ። በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሱ። የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ። እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ። በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ።"
(ኤፌ ፮፥፲፬-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ እና ለመነኮሳት አለቃ ቅዱስ መቃርስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ሰማዕት <3

ቅዱሱ ተወልዶ ያደገው በአንጾኪያ (ሶርያ) በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ነው። አባቱ ደግ ክርስቲያን የነበረ ሲሆን ስሙ ክርስቶፎሮስ ይባላል። "ለባሴ ክርስቶስ" እንደ ማለት ነው። እናቱ ግን ቴዎዳስያ የምትባል አረማዊት ነበረች። ምንም እንኳ አባቱ ክርስቲያን ቢሆን እናቱ ኃይለኛ የቤተ መንግሥት ሰው ስለነበረች በልጅነቱ አብሮኮሮንዮስ ክርስትናን ሊማር አልቻለም።

የልጁን አረማዊ መሆን ያልወደደ አባት አማራጩ አንድ ብቻ ነበር። እርሱም ወደ ጌታ መለመን ነበር። በእንዲህ ያለ ግብር ዘመናት ጐርፈው አብሮኮሮንዮስ ክርስቶስን ሳያውቅ ሃያ ዓመት ሆነው። እናቱ ወስዳ አሰልጥና ለጣዖት አምላኪ ንጉሥ ሰጠችው። ንጉሡም የጦር አለቃ አድርጐ ሾመውና አንድ ትዕዛዝ ሰጠው። "ክርስቲያኖችን ሁሉ ባገኘህበት ቦታ ጨፍጭፍ። ቤታቸውንም አቃጥል።"

አብሮኮሮንዮስ የታዘዘውን ሊፈጽም ሠራዊት አስከትሎ ሲወጣ ግን የአባቱ የሃያ ዘመናት ለቅሶና ጸሎት ፍሬ አፈራ። ገና መንገድ ላይ ሳለ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድምጹን ከሰማይ ላከለት። "ወደ እውነተኛ መንገድ ተመለስ። ካልሆነ ግን ሾተሉን ብትረግጥ ላንተ ይብስብሃል።" አለው።

አብሮኮሮንዮስም እየተንቀጠቀጠ "አቤቱ አንተ ማነህ?" አለው። ጌታም "ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ።" ሲል መለሰለት። ዳግመኛም "ምልክት ስጠኝ።" ቢለው የብርሃን መስቀል በሰማይ ላይ ገለጠለት። ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ጊዜ አላጠፋም።

ሠራዊቱን ይዞ ወደ ንጉሡ ከተማ ተመልሶ ንጉሡን በድፍረት አለው "እኔ ክርስቲያን ነኝ። ክርስቶስንም አመልካለሁ።" ካነጋገሩ የተነሳ አባቱን ደስ ሲለው ንጉሡና እናቱ ግን ደነገጡ። ንጉሡ ሊያስፈራራው ሞከረ። ግን አልተሳካለትም። ከዚያማ ያሰቃየው ገባ።

አንድ ቀን አካሉ እስኪቆራረጥ ገረፉት። በእሳትም አቃጠሉት። ሞተ ብለው አስበው ነበር። ወደ እርሱ ሲመለሱ ግን ጌታችን አድኖታልና የሰንበር ምልክት እንኳ በአካሉ ላይ አልተገኘም። እናቱ ቴዎዳስያ ከዚህ በላይ ምልክትን አልፈለገችም። በደቂቃዎች ልዩነት እርሷም ወደ ክርስትና ተመለሰች። ልጇንም ቀድማ ሐምሌ ፮ ቀን ሰማዕት ሆነች።

ቅዱስ አብሮኮርዮስን ግን ለበርካታ ጊዜያት አሰቃይተው ከክርስቶስ ፍቅር ሊለዩት ባለመቻላቸው በዚህች ቀን ገድለውታል። አባት፣ እናትና ልጅ (ክርስቶፎሮስ፣ ቴዎዳስያና አብሮኮሮንዮስ) ለሰማያዊ ርስት በቅተዋል። አባት ይሏችኋል እንዲህ ነው!

<3 ታላቁ ቅዱስ መቃርስ <3

በገዳማዊ ሕይወቱ እንደ ዘንባባ ያፈራው የመነኮሳት ሁሉም አለቃቸው ቅዱስ መቃርስ አንድ ቀን እንዲህ አደረገ።
አንድ በከተማ የሚኖር ባለ ጸጋ ስለ ቅዱስ መቃርስ ዝና ሰምቶ ሊባረክ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ይመጣል። አባ መቃርስ ባለ ጠጋው ወደ እርሱ እየመጣ መሆኑን ሲያውቅ በወንድሞች መነኮሳት መካከል ልብሱን ጥሎ እንደ አበደ ሰው አለል ዘለል እያለ ይጫወት ጀመረ።

ያ ከተሜ ባለ ጠጋ እንደ ደረሰ ወደ መነኮሳቱ ጠጋ ብሎ "የታላቁን መቃርስ ዝና ሰምቼ ልባረክ ነበር የመጣሁት። ከእናንተ መካከል ማንኛው ነው?" ቢላቸው "ያውልህ" ብለው አሳዩት። ሲያየው እንደ እብድና ሕፃን እየዘለለ ይጫወታል። ባለጠጋውም "ወይኔ! እኔኮ ደኅና ሰው መስሎኝ ነው። በከንቱ ደከምኩ።" ብሎ እያዘነ ሔደ። ወዲያው መነኮሳት ተሰብስበው ቅዱስ መቃርስን "ለምን እንደዚህ አደረግህ?" ቢሉት "መጀመሪያ እንደ ሰውነቴ ሊያከብረኝ ይገባል።" በሚል መልሷል። በርግጥም ከምንም ነገር በፊት ሰውን በሰውነቱ (በእግዚአብሔር አርአያ በመፈጠሩ) ብቻ ልናከብር ይገባል።

ታላቁ ቅዱስ መቃርስ በቤተ ክርስቲያን ዛሬ በዓሉ ይከበራል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃቸው ይማረን። ከበረከታችቸውም ያድለን።

ሐምሌ ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ሰማዕት
፪.ቅዱሳን ክርስቶፎሮስና ቴዎዳስያ (ወላጆቹ)
፫.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት አለቃ)
፬.ቅዱስ አሞንዮስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

"ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጐ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ። አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ። ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ። የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ።"
(፩ጢሞ ፩፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት የተአምር በዓልና ለሰማዕቱ አባ ሖር ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል <3

ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት ሁሉ አለቃቸው የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም በሆነ ተአምር ከከተማው ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ከመድኃኒታችን ክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመታት በፊት ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር። ደጋጉ ዳዊትና ሰሎሞን ካረፉ በኋላ የሕዝቅያስን ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእስራኤል ላይ አልነገሠም። ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም ነበር።

ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት። ወደ አካባቢውም መጥቶ ከቦ አስጨነቀው። ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር። በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከመቶ ሰማንያ አምስት ሺህ በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት።

"እገብርልሃለሁ፤ የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ። ነገር ግን ሃገሬን አታጥፋ። ኢየሩሳሌምን አታቃጥል፤ ሕዝቤንም አትግደል።" በሚል ለመነው። እጅ መንሻ ግብሩንም ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት።

ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእስራኤልን አምላክ ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ። ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ ማነው? ሕዝቡንም እግዚአብሔር ያድናል ብለህ አታታልላቸው።" ሲል ላከበት። ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ።

መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ። ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ አንደበት እንዲህ አለ "ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ።"

በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ። ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ። በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሣ ሠራዊቱ ሁሉ ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል።

በድንጋጤ ወደ ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት። ትዕቢተኛው ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ። ቅዱስ ሕዝቅያስ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖት የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት።

<3 ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት <3

ዳግመኛ በዚህ ቀን አባ ሖር ሰማዕቱ ይታሠባል።
ቅዱሱ፦
ስርያቆስ በምትባል የግብጽ አውራጃ ተወልዶ ያደገ፣
ገና በልጅነቱ መንኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፣
ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመነ፣
ከመኮንኑም ብዙ ስቃይ የደረሰበት፣
ብዙ ተአምራትን በመስራቱ ያሰቃየው የነበረውን መኮንን ወደ ክርስትና መልሶ ለሰማዕትነት ያበቃ አባት ነው።

እርሱም የሰማዕትነትን ክብር በእጅጉ ሽቷታልና ወደ ሌላ ሃገር ሒዶ በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀዳጅቷል። በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ያሳመናቸው መቶ ሃያ ሰባት ወንዶችና ሃያ ሴቶችም አብረውት ተሰይፈዋል።

እግዚአብሔር በሊቀ መላእክት ክንፍ ሃገራችንን ከአሕዛብ ስውር ጦር ይጠብቅልን። ከሰማዕቱም በረከት ያሳትፈን።

ሐምሌ ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሕዝቅያስ ንጉሥ
፪.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
፫.ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት
፬.መቶ አርባ ሰባት ሰማዕታት (የአባ ሖር ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፫.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ድሜጥሮስ
፭.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፮.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፯.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፰.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

"እግዚአብሔር ይላል 'ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ።'
በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ። ከአሦራውያንም ሠፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ። ማለዳም በተነሱ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ።"
(ኢሳ ፴፯፥፴፬-፴፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ናትናኤል <3

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ ሐዋርያ ነው።

ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእስራኤላውያን ወላጆቹ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው። ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ እርሱ ሕፃን እያለ ሔሮድስ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትን ሲፈጅ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል። እናቱ በቅርጫት ውስጥ አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው ነበር።

ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል። በባልንጀሮቹ ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ ስላደገ) አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር።

ምሑረ ኦሪት ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር። በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል የአጎት ልጅ ነው። ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ የጠራበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው።

ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ ከበለስ ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበር። "መሲሕ ምነው ቀረህ?" እያለም ይተክዝ ነበር። ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን አውቆ በፊልጶስ አማካኝነት ጠርቶታል።

ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር። በኋላ ግን የጌታችንን ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል። ጌታችንም "ክዳት ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እስራኤላዊ" ሲል አመስግኖታል።

ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያትን ተምሮ በጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሰክሮ ብዙ አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ ክርስቶስ) መልሷል። እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል።

የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም ሁለተኛ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ አገልግሏል። ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል። በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል። በገድለ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው በመቶ ሃምሳ ዓመቱ ነው። ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች በመጨረሻ ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል።

<3 አባ ብስንዳ <3

ዳግመኛ በዚህች ቀን ታላቁ አባ ብስንዳ ይታሠባል።
አባ ብስንዳ በዘመነ ጻድቃን ምድረ ግብጽ ውስጥ ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ነው። ቅዱሱን ከገድሉ ጽናት የተነሳ መላእክት በእጅጉ ይወዱት ነበር። "እኔ ልሸከምህ፤ እኔ ልሸከምህ።" እያሉ ይሻሙበት በተራ በተራም ተሸክመውት ይውሉ ነበር። እርሱም ለበርካታ ዓመታት ውኃ የሞላበት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ይጸልይ ነበር።

እንደ እሳት በሚባላው በረዶ ውስጥ ገብቶ መጸለዩ የፈጣሪውን ሕማማት ለመሳተፍና ለኃጥአን ምሕረትን ይለምን ዘንድ ነው። ሁሌም በዘጠኝ ሰዓት መላእክት ተሠብስበው ይመጡና በብርሃን ሠረገላ ይሸከሙታል። ከመሬትም ዘጠኝ ክንድ ከፍ ያደርጉት ነበር።
ከብዙ ዓመታት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሒዷል።

እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን። ከሐዋርያውና ከጻድቁ አባ ብስንዳ በረከትም አይለየን።

ሐምሌ ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ (ቀናተኛው ስምዖን)
፪.ታላቁ አባ ብስንዳ ጻድቅ
፫.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፭.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፮.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

"ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ' አለ። ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው። ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ።' አለው። ናትናኤልም መልሶ 'መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ። አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ።' አለው።"
(ዮሐ ፩፥፵፰-፶፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃን ወከዋክብተ ገዳም አቡነ ኪሮስ፣ አባ ብሶይና አባ ሚሳኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 አቡነ ኪሮስ ጻድቅ <3

የጻድቁን ስም የሚጠራ አፍ ንዑድ ነው፤ ክቡር ነው። በእውነት የቅዱሱን አባት ክብር ለማግኘት መፋጠን ይበጃል።

አቡነ ኪሮስ የተወለዱት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን ወላጆቻቸው ነገሥታት ናቸው። ተወልደው ባደጉባት ሃገር ቁስጥንጥንያ ገና በልጅነት ምቾት ሳያሳሳቸው መጻሕፍትንና ትሕርምትን ተምረዋል። ወንድማቸው (ታላቁ ቴዎዶስዮስ) በነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ ግፍ በዝቶ ነበርና አቡነ ኪሮስ ከኃጢአት ለመራቅና ለጌታ ለመገዛት ከከተማው ጠፍተው አሕጉር አቋርጠው ወደ ግብጽ (ገዳመ አስቄጥስ) መጡ።

እርሳቸውን ለመፈለግ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። ይባስ ብሎ የንጉሡ ልጅ ገብረ ክርስቶስ ሙሽርነቱን ጥሎ ወደ ሌላ ሃገር መነነ። "የቅኖች ትውልድ ይባረካል።" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት። አቡነ ኪሮስ ለሙሽራው ገብረ ክርስቶስ አጎቱ ናቸው። አቡነ ኪሮስ በገዳም ውስጥ የታላቁ አቡነ በብኑዳ ደቀ መዝሙር ሆነው ለዘመናት ቆይተዋል።

ቅዱስ በብኑዳን አንበሳ በበላው ጊዜ በጣም አዝነው "ለምን ጌታ ሆይ?" በሚል መሬት ላይ ወድቀው አለቀሱ። "ምክንያቱ ካልተነገረኝ አልነሳም።" ብለው ከወደቁበት መሬት ላይ ሳይነሱ ለአርባ ዓመታት አልቅሰዋል። በዚህ ምክንያት ግማሹ አካላቸው አፈር ሆኖ ሣር በቅሎበታል። ጌታችን ተገልጦ ምክንያቱን ነግሯቸዋል። አካላቸውንም እንደነበረ መልሶላቸዋል።

አንድ ቀን ጻድቁ ለቅዱስ በብኑዳ ሞት ምክንያት የሆነው መነኮስ ታንቆ መሞቱን ሰምተው በጣም አዘኑ። ሱባዔ ገብተው፣ ፍጹም አልቅሰው፣ ከጌታም አማልደው፣ የዚያን ኃጥእ ነፍስ ከሲዖል አውጥተዋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ኃጥአን የሞሉበት አንድ ገዳም በግብጽ ነበርና መቅሰፍት ወርዶ ሁሉንም በአንድ ቀን ሲያጠፋቸው አዩ።

ጻድቁ በዚህም ምክንያት ለሠላሳ ዓመታት አልቅሰው፣ ሙታኑን አስነስተው፣ ንስሐ ሰጥተው፣ ገዳሙን የጻድቃን ሕይወታቸውንም የፍቅር አድርገውታል። ጻድቁ እመቤታችንን ከመውደዳቸው የተነሳ በሥዕሏ ፊት አብዝተው ይሰግዱና ያለቅሱ ነበር። እመ አምላክም ተገልጣ ትባርካቸው ነበር።

ከዚህ በኋላ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሒደው ለሃምሳ ሰባት ዓመታት ማንንም ሳያዩ ተጋደሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና።) በየቀኑ ይጐበኛቸው ቁጭ ብሎም ያወራቸው ነበር። በመጨረሻም በዚህች ቀን ጌታ አእላፍ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ድንግል እመቤታችንና ቅዱስ ዳዊትን አስከትሎ ወረደ።

ቅዱስ ዳዊት ቀርቦ እያጫወታቸው በበገናው እየደረደረላቸው ከዝማሬው ጣዕም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች። ጌታችንም ታቅፎ ስሞ ይዟቸው አረገ። ሥጋቸውን አባ ባውማ ቀበሩት። የአቡነ ኪሮስ ቁመታቸው ቀጥ ያለ ጽሕማቸውም የተንዠረገገ ነበር። እድሜአቸውን ግን መገመት የሚቻል አይመስለኝም።

<3 የበርሃው ኮከብ አባ ብሶይ <3

ታላቁ አባ ብሶይ (ቢሾይ)፦
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ፣
በመላእክት መሪነት የመነኑ፣
የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ባልንጀራ፣
የአባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር የነበሩና በአጭር ጊዜ የብዙዎች አባት የሆኑ ሰው ናቸው።

እንቅልፍን የማያውቁ
በአርባ ቀን ብቻ እህል የሚቀምሱ፣
የጌታችንን እግር በየቀኑ እያጠቡ የሚመገቡ፣
ፈጣሪያቸውን በጀርባቸው ያዘሉ (ነዳይ መስሎ አግኝተውት)፣
በስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተጉና በርካታ ጻድቃንን የወለዱ ታላቅ የፍቅር ሰው ናቸው።

በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተው ቤተ ክርስቲያንን በንጽሕናቸው አስደስተው ሐምሌ ፰ ቀን ዐርፈዋል። ግብጽ ውስጥ የሚገኘው ገዳማቸው ዛሬም ቤተ አበው ተአምራት የማይለዩትና ተወዳጅ ነው። ቦታው መካነ ሱባዔ ወመንክራት ነውና።

<3 አባ ሚሳኤል ነዳይ <3

መቼም ያ ዘመን (አራተኛውና አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) እጅግ የተባረከ ነው። ቅዱሳኑ በብዛት የባለጸጐችና የነገሥታት ልጆች ናቸው። አባ ሚሳኤልም የኬልቄዶን ንጉሥ ልጅ ሳሉ መንነው በበርሃ ለስልሳ አምስት ዓመታት ተጋድለዋል። በመጨረሻ ግን በደዌ ምክንያት ወደቁ። ለአምስት ዓመታት መነኮሳቱ ሲጠይቋቸው ቆይተው ሰለቹ።

ከዚያም ለአሥራ አምስት ዓመታት ላበታቸው በግንባራቸው እየተቀዳ ያለ ምንም ምግብ እያቃሰቱ በበዓታቸው ወድቀው ኑረዋል። ቸሩ አምላክ ግን አራቱን ሊቃነ መላእክት (ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤልና ሳቁኤልን) አዝዞላቸው ሲጠብቋቸው ኑረዋል።

በዚህች ቀንም አቡነ ኪሮስ መጥተው አጽናንተው ጌታችንንም ጠርተው እንዲያርፉ አድርገዋል። መላእክት እያጠኑና እየዘመሩ ጻድቁ ቀብረዋቸዋል። በመቃብራቸውም ላይ ፈውስ የሆነ ጠበል ፈልቋል።

እግዚአብሔር የእኛን ያይደለ የጻድቃኑን ቅድስና አስቦ ይራራልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ሐምሌ ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ኪሮስ ጻድቅ (አረጋዊና ገዳማዊ)
፪.አባ ብሶይ ጻድቅ (ኮከበ ገዳም)
፫.አባ ሚሳኤል ነዳይ (ጻድቅ)
፬.አባ ቢማ ሰማዕት
፭.አባ በላኒ ሰማዕት
፮.ቅዱሳን አቤሮንና አቶም (ሰማዕታት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፫.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፬.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

"በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው። የኃጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። የጻድቅ መታሠቢያ ለበረከት ነው።"
(ምሳ ፲፥፮-፯)

"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና። ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና። ለዘለላምም ይጠብቃቸዋል። .....
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ መርቄሎስ እና ለነቢዩ ቅዱስ ዕዝራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ <3

ቅዱሱ በነገድ እስራኤላዊ የሆነ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ሰው ነው። ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር በምሥጢሩና በተአምራቱ ተማርኮ ተከትሎታል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ይሆን ዘንድ አድሎታል። ከጌታችን ሕማማትና ስቅለት በፊትም ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማስወጣት ከቻሉ አርድእትም አንዱ ነው።

ቅዱስ መርቄሎስ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለወንጌል አገልግሎት ተሰማርቷል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሠላሳ አራት ዓመታት በማገልገሉ ሐዋርያት ስሙን "ጳውሎስ" ብለውታል። ጳውሎስ ማለት ብርሃን ማለት ነውና። ልክ ሳውል "ጳውሎስ" እንደተባለው ማለት ነው።

ስሙ የግብር (በሥራ የሚገኝ) ስም ነው። በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን የምትጠራው "ጳውሎስ የተባለው መርቄሎስ" እያለች ነው።

ቅዱስ መርቄሎስ በ፷ዎቹ ዓ.ም አካባቢ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሮም ይሰብክ ነበር። ኔሮን ቄሳር ሊቀ ሐዋርያትን ዘቅዝቆ ሲሰቅለው የተመለከተና ይህንኑ የጻፈ እርሱ ነበር። ወታደሮቹ ቅዱስ ጴጥሮስን ገድለውት ሲሔዱ ቅዱስ መርቄሎስ እያነባ ቀርቦ ችንካሮችንም ነቅሎ ሊቀ ሐዋርያትን ከተሰቀለበት አወረደው።

በፍጥነት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ አምጥቶ በቅዱስ ጴጥሮስ ሥጋ ላይ አፈሰሰና በፍቅርና በክብር ሊገንዘው ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት አይኑን ግልጥ አድርጎ መርቄሎስን ተመለከተውና አለው፦ "ልጄ! ምነው ለእኔ ይህንን ያህል ሽቱ አባከንክ?" አለውና ተምልሶ ዐረፈ።

ቅዱስ መርቄሎስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በንጹሕ በፍታ ገንዞ እርሱ በሚያውቀው ቦታ ሠወረው። ሊቀ ሐዋርያትን በመገነዙ የክብር ክብር ተሰጥቶታል።

ቅዱሱ አሁንም ስብከተ ወንጌልን ቀጠለ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እርሱም ተይዞ በኔሮን ፊት ቀረበ። ኔሮን ቄሳር ቅዱስ መርቄሎስን ጠየቀው። "እንዴት ባለ አሟሟት ልግደልህ? እንደ መምህርህ ጴጥሮስ ወይስ ሌላ የምትፈልገው ዓይነት አሟሟት አለህ?"

ቅዱስ መርቄሎስ መለሰለት፦ "የትኛውም ዓይነት ሞት እኔን አያስፈራኝም። የምፈልገው ወደ ጌታዬ ቶሎ መሔድ ብቻ ነው።" አለው። ንጉሡ ኔሮንም ዘቅዝቃችሁ ስቀሉት አላቸው። ወታደሮቹም በዚህች ዕለት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል።

<3 ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ <3

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ፭፻ ዓመት አካባቢ የነበረ፣
እስራኤል ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ መጻሕፍት ተቃጥለው ጠፍተው ነበርና ስለ እነሱ አብዝቶ የለመነ፣
ጥበብን ሽቷልና እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን የላከለት፣
በሊቀ መላእክት እጅም ጽዋዐ ልቡናን የጠጣ፣
ብዙ ምሥጢራት የተገለጡለት፣
ለአርባ ቀናት ምግብ ሳይበላ ለአገልጋዮቹ የጠፉ መጻሕፍትን እየነገራቸው የጻፉለት፣
መጽሐፈ ዕዝራ የተሰኘ መጽሐፍን ያዘጋጀና
በብሉይ ኪዳን ከነበሩ ዐበይት ነቢያተ ጽድቅ አንዱ የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው።

ስለ ቅድስናውም ሞትን አልቀመሰም። በዚህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት ብሔረ ሕያዋን ውስጥ አስገብተውታል።

እግዚአብሔር ከሐዋርያውና ከነቢዩ በረከትን አይንሳን።

ሐምሌ ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
፪.ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅድስት ቴዎዳስያ ሰማዕት
፭.ቅድስት ንስተሮኒን ዘኢየሩሳሌም

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን ሁለተኛም ነቢያትን ሦስተኛም አስተማሪዎችን ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፣ እርዳታንም፣ አገዛዝንም፣ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል። ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን?
..... ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ።"
(፩ቆሮ ፲፪፥፳፰-፴፩)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባቶቻችን ቅዱሳን አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 አሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት <3

ነቢይ ማለት ከእግዚአብሔር ተመርጦ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን) መጻዕያትን (ለወደፊቱ የሚደረገውን) የሚያውቁ ሰዎች ሲሆኑ ሕዝቡን እንዲመሩ እንዲገስጹም ይላካሉ። ሕይወታቸውም በቅድስና የተለበጠ ነው። ነቢያትን በቁጥር መግለጽ ከባድ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን እንድንረዳቸው እንዲህ ትከፍላቸዋለች።
በኩረ ነቢያት አዳም
ሊቀ ነቢያት ሙሴ
ርዕሰ ነቢያት ኤልያስ
ልበ አምላክ ዳዊት
አሥራ አምስቱ ነቢያት (ከአዳም ጀምሮ እስከ ሳሙኤል)
አራቱ ዐበይት ነቢያት (ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል)
አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ደግሞ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉት ናቸው።

በዚህች ቀን ታዲያ አሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት በአንድነት ይታሠባሉ።
እነዚህም፦
፩.ቅዱስ ሆሴዕ (ኦዝያ)
፪.ቅዱስ አሞጽ
፫.ቅዱስ ሚክያስ
፬.ቅዱስ ኢዩኤል
፭.ቅዱስ አብድዩ
፮.ቅዱስ ዮናስ
፯.ቅዱስ ናሆም
፰.ቅዱስ እንባቆም
፱.ቅዱስ ሶፎንያስ
፲.ቅዱስ ሐጌ
፲፩.ቅዱስ ዘካርያስና
፲፪.ቅዱስ ሚልክያስ ናቸው።

ቅዱሳኑ ደቂቀ ነቢያት የተባሉት
፩.የነቢያት ልጆች በመሆናቸው
፪.የጻፏቸው ሐረገ ትንቢቶች በንጽጽር ከዐበይቱ (ከነ ኢሳይያስ) ስለሚያንስ ነው።

በምግባር፣ በትሩፋትና በአገልግሎት ግን ያው ናቸው። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እሊህን ነቢያት "እለ አውኀዙ ተነብዮ በእንተ ስመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ" ይሏቸዋል።
ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መውረድ፣ መወለድና የማዳን ሥራ የትንቢት ጐርፍን ያፈሰሱ እንደ ማለት ነው።

ቅዱሳኑ ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ባሻገር ዓለማችን ላይ ከነበሩበት ዘመን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሊደረጉ ያላቸውን ነገሮችም ተናግረዋል። የነበሩበት ዘመን በአማካኝ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከዘጠኝ መቶ እስከ አምስት መቶ ነው። በትንቢት ደረጃም እንደነ ሆሴዕና ዘካርያስ አሥራ አራት ምዕራፎችን እንደነ አብድዩም አንዲት ምዕራፍ ብቻም የጻፉ አሉ።

በሕይወታቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያሻቸው ናቸውና በየጊዜው ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገሩ የእርሱን ድምጽ ለእስራኤል (አንዳንዴም ለአሕዛብ) ያደርሱ ነበር። ፊት አይተው የማያዳሉ ናቸውና ሕዝቡንም ሆነ ነገሥታቱን ስለ ኃጢአታቸው ይገሰጹ ነበር። በዚህም ምክንያት ከነገሥታቱና ከሕዝቡ አለቆች መከራ ደርሶባቸዋል። አልፎም ያለ አበሳቸው ሕዝቡ በኃጢአቱ ሲማረክ አብረውት ወርደዋል።

በመጨረሻ ሕይወታቸውም አንዳንዶቹን ክፉዎች ሲገድሏቸው አንዳንዶቹ ደግሞ በመልካም ሽምግልና ዐርፈዋል። ዛሬ ነቢያት ከእነርሱ ባሕርይ በተገኘችና ብዙ ትንቢትን በተናገሩላት በእመቤታችን ምክንያት ክርስቶስ ድኅነትን ፈጽሞላቸው በተድላ ገነት ይኖራሉ። ስለ እኛም ይማልዳሉ።
"ናጥሪ እንከ ትሕትና ዘምስለ ንጽሕና - እንግዲህ እንደ ነቢያት ትሕትናን ከንጽሕና ጋር ገንዘብ እናድርግ"

"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ - ነቢያት መንፈስን ንጹሕ በማድረግ እግዚአብሔርን አይተውታልና፤ ፊት ለፊትም ተያይተዋልና።"
(ቅዳሴ ማርያም)

ከአባቶቻችን ቅዱሳን ነቢያት በረከት ይክፈለን።

ሐምሌ ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት
፪.ቅዱስ ሶፎንያስ ነቢይ (ዕረፍቱ)
፫.ቅዱሳን ሰማዕታት አቡቂርና ዮሐንስ (ቅዳሴ ቤታቸው)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ (ወንጌላዊው)
፪.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

"ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት። በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሠከረ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር።"
(፩ጴጥ ፩፥፲-፲፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃን እንድራኒቆስ ወአትናስያ እና ለአቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጻድቃን እንድራኒቆስ ወአትናስያ <3

ሁለቱ ቅዱሳን ባል እና ሚስት (ባለትዳር) ናቸው። የነበሩበት ዘመን አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። እስኪ እግዚአብሔር የቀደሰው ጋብቻ ምን እንደሚመስል እንመልከት።

እንድራኒቆስና አትናስያ በዘመናቸው ከልጅነት ጀምረው ቃለ እግዚአብሔርን የሚሰሙ ለወላጆቻቸው የሚታዘዙ ነበሩ። ዘመኑ ደርሶ በሚገባው የተክሊል ሥርዓት ጋብቻቸውን ፈጸሙ። አርባ ቀን ከተፈጸመ በኋላ ከምንም ነገር በፊት ሁለቱ ቁጭ ብለው ተወያዩ።

የውይይታቸው ርዕስ ደግሞ "ፈጣሪያችንን በምን እናስደስተው።" የሚል ነበር:: ውይይታቸው የተጠናቀቀው በእነዚህ ውሳኔዎች ነው።
፩.ሁልጊዜም እንግዳ መቀበል አለብን።
፪.ነዳያን ከቤታችን ሊጠፉ አይገባም።
፫.ጸሎት፣ ጾምና ስግደት በቤት ውስጥ አይቋረጥም።
፬.አብሮ ለመተኛት መቸኮል የለብንም።

እነርሱ መልካምን አስበዋልና አምላክ የሰጣቸውን ሃብት ሲመጸውቱ ኖሩ። ከዘመናት የቅድስና ጉዞ በኋላ በፈቃደ እግዚአብሔር ሁለት ልጆችን አከታትለው ወለዱ። ወንዱን "ዮሐንስ" ሴቷን ደግሞ "ማርያም" አሏት።

እነርሱን ከወለዱ በኋላ እንደ ገና ሌላ ውሳኔ አሳለፉ። "ይህንን ላደረገልን ጌታ ከዚህ በኋላ አልጋ እንለያለን።" ብለው ለአሥራ ሁለት ዓመታት በጾምና በጸሎት ተወሰኑ።

ሕፃናቱ ዮሐንስና ማርያም በቅንነት አድገው እድሜአቸው አሥራ ሁለት ሲሆን ሁለቱም በአንድ ቀን ታመው ሞቱ። ይህ ለአንድ ወላጅ የመጨረሻው አሰቃቂ ፈተና ነው። ሁለቱም (እንድራኒቆስና ሚስቱ አትናስያ) ልጆቻቸውን ታቅፈው ወስደው ቀበሩ።

እንድራኒቆስ ከቀብር በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ግን እንዲህ አለ፦
"አምላከ ኢዮብ! አንተ ሰጠኸኝ። አንተም ነሳኸኝ። ስምህ ለዘላለም ይባረክ።" ብሎ ሔደ። እናት አትናስያ ግን ከሐዘን ብዛት ልቡናዋ ሊሠወር ጥቂት ቀረው።

የልጆቿ መቃብር ላይ ተደፍታ ስታለቅስ ቅዱስ መልአክ ልቡናዋን ወደ ሰማይ አሳረገው። ልጆቿ ዮሐንስና ማርያም በገነት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ሐሴትን ሲያደርጉም ተመለከተች። ወዲያው ወደ ቤት ተመልሳ ለባሏ እንድራኒቆስ ያየችውን ነገረችውና ደስ አላቸው።

እዚያው ላይ "ለዚህ ውለታው ከነፍሳችን ውጪ የምንሰጠው የለም።" ብለው ሊመንኑ ተስማሙ። እጅግ ሃብታሞች ነበሩና ነዳያንን ሰብስበው ሃብት ንብረታቸውን ቤት ርስታቸውን አካፍለው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሔዱ።

እርሷ ከሴቶች ገዳም እርሱ ደግሞ ከወንዶቹ ገቡ። ለአሥራ ሁለት ዓመታት በፍጹም ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ተገዙ። በእነዚህ ዘመናት ተያይተው አንዱ ስለ ሌላው ሰምቶ አያውቅም። በጸሎት ግን ያለማቋረጥ ይተሣሠቡ ነበር።

ከአሥራ ሁለት ዓመታት በኋላ የፍቅር አምላክ በሁለቱም ልቡና በተመሳሳይ ሰዓት ተመሳሳይ ሐሳብን አመጣ። እርሱ ከአበ ምኔቱ (ታላቁ አባ ዳንኤል) እርሷም ከእመ ምኔቷ አስፈቅደው ወደ ኢየሩሳሌም ከቅዱሳት መካናት ለመባረክ ጉዞ ጀመሩ። በየፊናቸው ጥቂት እንደተጓዙ እርስ በእርስ ተያዩ።

እርሷ ለየችው። እርሱ ግን ጭራሽ ሊለያት አልቻለም። ይህም ጥበበ እግዚአብሔር ነው። ሁለቱም እየተጫወቱ እየጸለዩ በሰላም ተባርከው ወደ ግብጽ ተመለሱ። በእነዚህ ጊዜያት ቅድስት አትናስያን የሚለያት አልነበረም። አካሏ በገድል ከመለወጡ ባሻገር የለበሰችው እንደ ወንድ መነኮሳት ነበር።

ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሲደርሱ ጸጋው ተሰጥቶታልና አባ ዳንኤል ባልና ሚስት መሆናቸውን አወቀ። "ለምን አብራችሁ አትኖሩም?" አላቸው። "እኛ ደስ ይለናል።" አሉት። ከዚያ እርሷ እያወቀችው እርሱ ሳያውቃት ለአሥራ ሁለት ዓመታት አብረው በቅድስና ኖሩ።

ከእነዚህ ዘመናት በኋላ ግን ሐምሌ ፳፰ ቀን ቅድስት አትናስያ ታመመች። አባ ዳንኤል ሥጋውን ደሙን አቀብሏትም ዐረፈች። ሊገንዟት ሲቀርቡ ቅዱስ እንድራኒቆስ መልኳን ልብ ቢለው ሚስቱ ናት።

በአንድ ጊዜ ሚስቱንና የሚወደውን ባልንጀራ በማጣቱ አለቀሰ። እርሷን ቀብረው ወደ በዓቱ ተመልሶ "ጌታ ሆይ! ውሰደኝ?" አለ። እርሱም ተከትሏት ዐረፈ። አባ ዳንኤል እርሱንም ቀብሮ ጥዑም ዜናቸውን ጻፈ።

<3 አባ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ <3

ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ፣ ሐዋርያና ሰማዕት አቡነ ፊልጶስ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሲሆኑ የተወለዱት በምድረ ሽዋ በ፲፪፻፷፮ ዓ.ም ነው። ከልጅነታቸው ጀምረው ምሥጢር ተመራማሪና መጻሕፍትን መርማሪ የነበሩት ጻድቁ የመነኑት ገና በአሥራ አምስት ዓመታቸው ነበር።

በደብረ ሊባኖስ በአሞክሮ ለሦስት ዓመታት ቆይተው መንኩሰዋል። ለሃያ ሁለት ዓመታትም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው አገልግለዋል። አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ፲፫፻፮ ዓ.ም ነሐሴ ፳፬ ቀን ሲያርፉ የተተኩት አባ ኤልሳዕ ቢሆኑም ለሦስት ወራት ቆይተው ዐርፈዋል።

በ፲፫፻፯ ዓ.ም አቡነ ፊልጶስ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት (እጨጌ) ሁነዋል። ገዳሙንም ለሃያ ስምንት ዓመታት መርተዋል። ከዚያም በዘመነ አፄ ዓምደ ጽዮንና በአፄ ሰይፈ አርዕድ ብዙ ስደት፣ መከራ፣ እሥራትና ግርፋት ደርሶባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ እውነትን መናገራቸውና ነገሥታቱን መገሰጻቸው ነበር። በስደትም ለስድስት ዓመት ከዘጠኝ ወር ቆይተዋል።

ሃገሪቱን በስብከተ ወንጌል ካበሩ አሥራ ሁለቱ ንቡራነ እድ አንዱ የሆኑት እጨጌ አባ ፊልጶስ በተወለዱ በሰባ አራት ዓመት ከዘጠኝ ወራቸው በ፲፫፻፵፩ ዓ.ም ዐርፈዋል። የተቀበሩት በደብረ ዕንቁ ሲሆን ካረፉ በመቶ አርባ ዓመት አቡነ መርሐ ክርስቶስ ዐጽማቸውን አፍልሰዋል።

ከቅዱሳኑ እንድራኒቆስ ወአትናስያና ከጻድቁ አቡነ ፊልጶስ በረከትን ይክፈለን።

ሐምሌ ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ጻድቃን እንድራኒቆስና አትናስያ
፪.አቡነ ፊልጶስ ጻድቅ (ዘደብረ ሊባኖስ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፫.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

"ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል። ከሚስቱም ጋር ይተባበራል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው። እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጐ ይውደዳት። ሚስቱም ባሏን ትፍራ።"
(ኤፌ ፭፥፴፩-፴፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን፣ ለአረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ እና አባ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን <3

ቅዱሱ በትውልዳቸው ግሪካዊ ቢሆኑም ሶርያ አካባቢ እንዳደጉ ይታመናል። በቀደመ ስማቸው ፍሬምናጦስ የሚባሉት አቡነ ሰላማ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በአደጋ ምክንያት (በድንገት) ቢመስልም ውስጡ ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረበት።

በድንበር ጠባቂዎች (በአደጋ ጣዮች) ከባልንጀራቸው ኤዴስዮስ ጋር ተይዘው ወደ አክሱም የመጡት በንጉሥ ታዜር (አይዛና) እና በሚስቱ ሶፍያ (አሕየዋ) ዘመን ነው። ጊዜው በውል ባይታወቅም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው።

ፍሬምናጦስ ምንም የመጡበት ዓላማ ስብከተ ወንጌል ባይሆንም በአክሱም ቤተ መንግሥት አካባቢ ይሰበኩ ነበር። ያን ጊዜ በጃንደረባው ቅዱስ ባኮስ የተቀጣጠለው የክርስትና ችቦ ውስጥ ውስጡን በሃገሪቱ ነበረና ፍሬምናጦስ አልተቸገሩም። በተለይ ሕፃናቱን (ኢዛናና ሳይዛናን) ገና ከልጅነት ስላስተማሯቸው ነገሮች የተሳኩ ሆኑ።

ልክ ንጉሥ ታዜር እንደ ሞተ ሁለቱ ሕፃናት በመንበሩ ተቀመጡ። ፍሬምናጦስንም ወደ ግብጽ ጳጳስና ጥምቀት ከመጻሕፍት ጋር እንዲመጣላቸው ላኩ። ሐዋርያዊ ቅዱስ አትናቴዎስም ፍሬምናጦስን "ሰላማ" ብሎ ሰይሞ በጵጵስና፣ በንዋየ ቅድሳትና በመጻሕፍት ሸልሞ መለሳቸው።

አቡነ ሰላማ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ ከነገሥታቱ ጀምረው ለሕዝቡ ጥምቀትን አደሉ። ኢዛናና ሳይዛናም አብርሃ (አበራ) እና አጽብሃ (አነጋ) ተብለው ስማቸው ተደነገለ። ከዚያ በኋላ ድንቅ በሚሆን አገልግሎት ነገሥታቱ፣ ጳጳሱ ሰላማና ሊቀ ካህናቱ እንበረም ለክርስትና መስፋፋት በጋራ ሠርተዋል።

የአቡነ ሰላማ ትሩፋቶች፦
፩.ጵጵስናና ክህነትን ከእውነተኛ ምንጭ አምጥተዋል።
፪.ክርስትናና ጥምቀትን በሃገራችን አስፋፍተዋል።
፫.ቅዱሳት መጻሕፍትን ከውጭ ልሳኖች ተርጉመዋል።
፬.ገዳማዊ ሕይወትን ጀምረዋል።
፭.አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል።
፮.ግዕዝ ቋንቋን አሻሽለዋል።
ሀ.ከግራ ወደ ቀኝ እንዲፃፍ፣
ለ.እርባታ እንዲኖረውና
ሐ.ከ"አበገደ" ወደ "ሀለሐመ" ቀይረዋል።

ባላቸው ንጹሕ የቅድስና ሕይወት ለሕዝቡ ምሳሌ ሆነዋ። "ወበእንተዝ ተሰይመ ከሳቴ ብርሃን" እንዲል ገድላቸው በእነዚህ ምክንያቶች "ከሣቴ ብርሃን" (ብርሃንን የገለጠ) ሲባሉ ይኖራሉ። በመጨረሻም ከመልካሙ ገድል በኋላ በ፫፻፶፪ ዓ.ም ዐርፈው ተቀብረዋል።

<3 ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ <3

በሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ አካባቢ ስም አጠራራቸው ከከበረ ደጋግ እስራኤላውያን አንዱ የእመቤታችን ጠባቂ ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ ነው። ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ ሲሆን አባቱ ያዕቆብ ይሰኛል።

በጉብዝናው ወራት የእመቤታችንን አክስት ማርያምን አግብቶ ብዙ ልጆችን ወልዶ አርጅቷል። ከልጆቹም ዮሳ፣ ያዕቆብ፣ ይሁዳ፣ ስምዖንና ሰሎሜ በቅዱስ መጽሐፍ ተዘክረዋል። ቅዱስ ዮሴፍ እድሜው ሰባ አምስት ሲሆን ሚስቱ ማርያም ሞተችበት።

ከጥቂት ወራት በኋላም በመንፈስ ቅዱስ ድንግል ማርያምን ሊያገለግል ተመረጠ። "እጮኛ" የሚለውም ለዚያ ነው። (ለአገልግሎት ነው የታጨው) እመቤታችን ለአረጋዊ ዮሴፍ በሁለት ወገን ልጁ (ዘመዱ) ናት።
፩.የሚስቱ ማርያም የእኅት (የሐና) ልጅ ናት።
፪.የቅድመ አያቱ የአልዓዛር የልጅ ልጅ ናት።

ደጉ ሽማግሌ ቅዱስ ዮሴፍ ምን ቢያረጅ እመቤታችንን ለማገልገል አልደከመውም። አብሯት ተሰደደ፣ ረሃብ ጥማቷን፣ ጭንቅና መከራዋን፣ ሐዘንና ችግሯን ተካፍሏል። ከእመ ብርሃንና አምላክ ልጇ ጋር ለአሥራ ስድስት ዓመታት ኑሯል።

ከእነዚህ ዘመናት በኋላም በ፲፮ ዓ.ም በተወለደ በዘጠና አንድ ዓመቱ ሲያርፍ ጌታችን "ሥጋህ አይፈርስም።" ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶለታል።
"ኢየሱስ ክርስቶስ በከመ አሠፈዎ ኪዳነ
ኢበልየ በመቃብር ወኢሂ ማሰነ
እስከ ዮም በድኑ ሐለወ ድኁነ።" እንዳለ መጽሐፈ ስንክሳር።

<3 ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት <3

ይህ ቅዱስ አባት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረ አባት ነው። ዘመነ ሲመቱም ከ፫፻፸፯ ዓ.ም እስከ ፫፻፹፯ ዓ.ም ድረስ ለአሥር ዓመታት ነው። በእነዚህ ዘመናቱ "ዘአልቦ ጥሪት" (ገንዘብ የሌለው/ነዳዩ አባት) ነበር የሚባለው። ገንዘብንና ዓለምን የናቀ አባት ነበር።

ቅዱስ ጢሞቴዎስ የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ደቀ መዝሙር እንደ መሆኑ ከመንፈሳዊ አባቱ መልካም ሕይወትን ወርሷል። ምሥጢራትንም አጥንቷል። በዘመኑ የአርዮስ ውላጆች ቤተ ክርስቲያንን ያስቸግሩ ነበርና ከእነርሱ ጋር ተዋግቷል። ምዕመኑንም ከተኩላዎች ይጠብቅ ዘንድ ተግቷል።

በ፫፻፹፩ ዓ.ም በቁስጥንጥንያ ጉባዔ በተደረገ ጊዜ ማኅበሩን በሊቀ መንበርነት መርቷል። ለመቅዶንዮስ፣ ለሰባልዮስና ለአቡሊናርዮስ ኑፋቄዎችም ተገቢውን ምላሽ ሰጥቶ አውግዟል። ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት በቅድስና ተመላልሶ በ፫፻፹፯ ዓ.ም በዚህች ቀን ዐርፏል።

ፈጣሪ ከአቡነ ሰላማ፣ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከቅዱስ ጢሞቴዎስ በረከትን ያሳትፈን።

ሐምሌ ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
፪.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ (የድንግል ማርያም ጠባቂ)
፫.ቅዱስ አባ ጢሞቴዎስ (ዘአልቦ ጥሪት)
፬.አባ ሮዲስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን

"እናንተ የምድር ጨው ናችሁ።..... እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል። በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።"
(ማቴ ፭፥፲፫-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ዘዮሐንስ እና ለሰማዕቱ አባ ኖብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ <3

ኢትዮጵያዊው ጻድቅ የተወለዱት በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሸዋ (መርሃ ቤቴ) ነው። ወላጆቻቸው ዘካርያስና ሶፍያ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ እመ ብርሃንን የሚወዱና ለነዳያን የሚራሩ ነበሩ።

ደጉ ዘካርያስ መስፍን ሲሆን እርሱ በሌለበት የሸዋ ገዢ ሊያገባት በመሞከሩ ቅዱስ ገብርኤል ቀስፎታል። ሕዝቡ ገዢነቱን ለዘካርያስ ሰጥተውታል። ከቆይታ በኋላም ድንግል ማርያም የተባረከ ፍሬ ሰጠቻቸው። ስሙን "ዮሐንስ" አሉት። በሒደት ግን ዘዮሐንስ (የዮሐንስ) ተብሏል።

ቅዱሱ ዘዮሐንስ እስከ ሰባት ዓመቱ ድረስ በእናቱ እቅፍ ቆይቶ ወደ ትምህርት ገብቷል። ጸጋ እግዚአብሔር ጠርቶታልና በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ። አደን ይወድ ነበርና ሊያድን ሲወጣ 'ብርሕት ደመና' ድንገት ነጥቃ ከኢትዮጵያ (ሽዋ) ወደ ኢየሩሳሌም (ጐልጐታ) አደረሰችው።

ደስ ብሎት ቅዱሳት መካናትን ተሳልሞ ደመናዋ ወደ ሃገሩ መለሰችው። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከሰማይ ነቢዩ ኤልያስና መጥምቁ ወርደው ባረኩትና "ክፍልህ ከእኛ ጋር እንዲሆን መንን።" አሉት።

ዘዮሐንስ ወላጆቹንና ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ (ዲቁና ነበረውና) ሃያ አምስት ዓመት ሞላው። ያን ጊዜ ወላጆቹ "እንዳርህ?" ቢሉት "የለም! አይሆንም።" አላቸው። አርጅተው ነበርና ስለእነርሱ ዕረፍት ጸለየ። ፈጣሪም ሰምቶታልና ሁለቱም በክብር ተከታትለው ዐረፉ።

ሕዝቡ በወላጆቹ ፈንታ "እንሹምህ።" ቢሉት "እንቢ" ብሎ ወርቁን፣ ብሩን፣ ርስቱን፣ ቤቱን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገባ።
ጊዜው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ባረፉ በሃምሳ ዓመት አካባቢ ሲሆን አባ ሕዝቅያስ አበ ምኔት ነበሩ።
(ከዚህ በኋላ አንቱ እያልን እንቀጥል።)

አባ ዘዮሐንስ ለሰባት ዓመታት ገዳሙን ረድተው መነኮሱ። እንደ ልማዱ ደመና ነጥቆ ወስዷቸው ከኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ቅስና ተቀብለዋልና በደብረ ሊባኖስ ለሃያ አምስት ዓመታት አገለገሉ። ቤተ መቅደሱን በመዓልት ሰባት ጊዜ በሌሊት ሰባት ጊዜ ያጥኑ፣ እልፍ እልፍ ይሰግዱ፣ ተግተው ይጸልዩ፣ ይታዘዙም ነበር።

ከዚያም በፈጣሪ ትዕዛዝ በትግራይና በሌሎቹ የሃገራችን ክፍሎች ወንጌልን ሰብከዋል። እድሜአቸው ሰባ በሆነ ጊዜ ወደ ጌታ መቃብር (ጐልጐታ) ሔደው ተሳልመው በእርሱ (በጌታ) ትዕዛዝ ወደ ደራ (ጣና ዳር) ተመለሱ።

በአካባቢውም ገብርኤልና መስቀል ክብራ የሚባሉ ደጋግ ባለ ትዳሮች ነበሩና በእንግድነት ከቤታቸው አደሩ። ቤቱ በቅጽበት በበረከት ሞላ። እነርሱም የጻድቁን አምላክ አመሰገኑ።

ቀጥሎም በመስቀል ክብራ መሪነት ጻድቁ ዘዮሐንስ ወደ ክብራን ገብርኤል ደሴት ገቡ። (በነገራችን ላይ ደሴቱ ክብራን የተባለ መስቀል ክብራ በምትሰኘው ደግ ሴት ስም ነው። እርሷና ባሏ ገብርኤል የተቀደሱ ሰዎች ነበሩና።)

ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ ወደ ደሴቶቹ (ክብራንና እንጦንስ ኢየሱስ) እንደ ገቡ ደሴቶቹ በግማሹ የስውራን ቤት እኩሉ ደግሞ የጣዖት (ዘንዶ) አምላኪዎች መኖሪያ ነበር። ጻድቁ ክብራን ገብርኤልንና እንጦንስ ኢየሱስን የመሠረቱት በ፲፫፻፲፭ ዓ.ም አካባቢ በዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመን ነው። በአካባቢው ዘንዶ ይመለክ ነበርና ያንን በጸሎታቸው አጥፍተው ሕዝቡን አጥምቀዋል።

በዚያም ገዳሙን የወንድና የሴት ብለው ከፈሉ። የወንዶች ክብራን ሲሆን ሴት አይገባበትም። አበ ምኔቱም ራሳቸው ጻድቁ ነበሩ።
የሴቶች እንጦንስ ኢየሱስ ከካህናት በቀር ወንድ አይገባበትም። እመ ምኔቷም እናታችን ቅድስት ክብራ (መስቀል ክብራ) ሆነች።

ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ በክብራን ለሠላሳ አምስት ዓመታት ተጋድለዋል። ለጸሎት ከመቆማቸው ብዛት እግራቸው አብጦ ቆሳስሎ ነበር። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ይገለጽላቸው ያነጋግራቸውም ነበር።

እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ሠርተው ለወንጌል እንደሚገባ ኑረው በተወለዱ በመቶ አምስት ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። ጌታችንም በስማቸው ለተማጸነና ገዳማቸውን ለሳመ የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ልደታቸው ደግሞ ኅዳር ፲፫ ቀን ይከበራል። ገዳማቸው (ክብራን ገብርኤልና እንጦንስ ኢየሱስ) ድንቅ ነውና እንድታዩት ተጋብዛችኋል።

<3 ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት <3

በምድረ ግብጽ ከታዩ ታላላቅ ከዋክብት አንዱ ቅዱስ ኖብ በሃገረ ንሒሳ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ዘመኑም ዘመነ ሰማዕታት (ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ነው። ወላጆቹ በልጅነቱ ብዙ ሃብት ትተውለት ያርፋሉ። ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ካህኑ ስለ ምናኔና ሰማዕትነት ሲሰብክ ይሰማዋል።

ገና በአሥራ ሁለት ዓመቱ በቤቱ የነበረውን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ መስቀለ ክርስቶስን ሊሸከም ወደ ዐውደ ስምዕ (የምስክርነት አደባባይ -የክርስቲያኖች መገደያ ቦታ) ተጓዘ። በዚያም በጉባዔ መካከል ክርስቶስን ሰበከ። በዚህ ምክንያት በሰብዓዊ አካል ሊሸከሙት የማይችሉትን መከራ በልጅ ገላው ተቀብሏል።

በዚያው ልክም ብዙ ተአምራትን ሠርቷል። በተአምራቱና በጣዕመ ስብከቱም ከመቶ ዘጠና ሺህ በላይ አሕዛብን ወደ ክርስትና መልሶ ሁሉም ተሰይፈዋል። በእሳት፣ በስለት፣ በሰይፍ፣ በባሕርና በየብስ መከራን ከተቀበለ በኋላ በዚህች ቀን አክሊለ ክብርን ይቀበል ዘንድ አንገቱን ተከልሏል።

ጌታችን የገባለት ቃል ኪዳኑ ግሩም ነውና ዛሬ በግብጽ በድምቀት ይከበራል። ምንም በእድሜ ልጅ ቢሆን ቤተ ክርስቲያን አባ (አባታችን) ኖብ ትለዋለች።

ቸር ጌታ መድኃኔ ዓለም በጻድቁና በሰማዕቱ ጸሎት ይማረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ሐምሌ ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን (ኢትዮጵያዊ)
፪.ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት
፫.መቶ ዘጠና ሺህ ሰማዕታት (የአባ ኖብ ማኅበር)
፬.አባ ተክለ አዶናይ ዘደብረ ሊባኖስ
፭.አቡነ ተወልደ መድኅን (ኢትዮጵያዊ)
፮.አባ ስምዖን ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
፯.ቅድስት ክብራ (መስቀል ክብራ) ዘእንጦንስ ኢየሱስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤጲስቆጶስ)
፫.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮.ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል)
፯.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮጵያዊ)

"ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም።"
(ኤፌ ፩፥፲፭-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእናታችን ቅድስት መሪና ሰማዕት እና ቅዱስ ለንጊኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቋ ቅድስት መሪና ሰማዕት (SAINT MARINA THE GREAT) <3

እናታችን ቅድስት መሪና ስም አጠራራቸው ከከበረ ተጋድሏቸው ካማረ ታላላቅ ሴት ሰማዕታት አንዷ ናት። ተወልዳ ያደገችው ከዋናው ዘመነ ሰማዕታት በፊት በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሶርያ አካባቢ ነው። አባቷ ዳኬዎስ የሚባል ጣዖት አምላኪ ቢሆንም እናቷ ግን ክርስቲያን ነበረች።

ነገር ግን እናቷ ገና በአምስት ዓመቷ ሞተችባትና ለሞግዚት ተሰጠች። የእግዚአብሔር ጥበብ ሆኖ ሞግዚቷ ደግ ክርስቲያን ነበረችና ለአሥር ዓመታት ሃይማኖተ ክርስቶስን እና ምግባረ ጽድቅን አስተማረቻት። ዕድሜዋ አሥራ አምስት ዓመት ሲሆን አባቷ ዳኬዎስ ዐረፈ።

በዘመኑ ዳኬዎስ የሚሉት (ቅዱስ መርቆሬዎስን የገደለው) ክፉ ንጉሥ ነበርና ክርስቲያኖችን አሳደዳቸው። ይህን ዜና ቅድስት መሪና ስትሰማ ደስ አላት። እጅግ ባማረ ንጽሕና እንደ ኖረች ሁሉ በክርስቶስ ስም ደሟን ለማፍሰስ አስባ ወደ ንጉሡ መኮንን ሔደች።

አበው እንዳስተማሩን ከሴቶች ሰማዕታት በውበትና ደም ግባት እንደ ቅዱሳት መሪና፣
አርሴማና
ጣጡስ የሚያክል የለም። ዓይንን ማፍዘዝ የሚችል ውበት ነበራቸው።

መኮንኑ መልኳን ዐይቶ ሰውነቱ ተናወጠ። "ጣዖት አምልኪና የእኔ ሚስት ሁኚ?" አላት። እርሷ ግን መኮንኑን ከነ ጣዖቱ አቃለለችው። "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ።" አለችው።

መኮንኑ ካነጋገሯ የተነሳ ተቆጥቶ ይገርፏት ዘንድ አዘዘ። መሬት ላይ ጥለው በብረት ዘንግ ቢመቷት አካሏ እየተቆረጠ ብዙ ደም ፈሰሰ። ወስደውም ጨለማ ውስጥ ጣሏት። ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ አድኗት አጽንቷትም ዐረገ።

በማግስቱ በመጋዝ አካሏን ቆራርጠው ጣሉ። ዳግመኛ ሊቀ መላእክት አዳናት። ወደ ጨለማ ክፍል ወስደው ሲጥሏት ትልቅ ዘንዶ መጣባት። እጆቿ ተዘርግተው እየጸለየች ዋጣት። እርሷ ግን ጸሎቷን ቀጠለች። ከደቂቃዎች በኋላ ግን ዘንዶው ለሁለት ተሰነጠቀና እጆቿ እንደተዘረጉ ወጣች።

በሌላ ቀን ግን ሰይጣን ፊት ለፊት መጥቶ ታገላት። ከሰማይ ነጭ ርግብና መስቀል ወርዶላታልና አልቻላትም። ከእግሯ በታች ጥላ ደጋግማ ረገጠችው። ሰይጣንም በሐፍረት እየጮኸ ሔደ።
"ለሰይጣን ኬደቶ ከመ አሣዕን በእግር" እንዲል። (እንዲህ ነበሩ የቀደመው ዘመን እናቶቻችን።)

መኮንኑ ከክርስትና ያስወጣት ዘንድ በትልቅ ጋን ውኃ አስፈልቶ "በዚያ ላይ ቀቅሏት።" አለ። ድንገት ግን ከሰማይ ነጭ ርግብ ወርዳ ውኃውን አቀዝቅዛ ሦስት ጊዜ በውኃው አጠመቀቻት። (እስከዚህ ሰዓት ድረስ አልጠመቀችም ነበርና።)

ርግቧ የብርሃን ልብስ አልብሳ አክሊለ ክብር ደፋችላት። መኮንኑ ተስፋ ስለ ቆረጠ "አንገቷን በሰይፍ ምቱ።" አለ። በዚያች ሰዓት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ "ብጽዕት መሪና ብጽዐን ይገባሻል።" አላት።

"ስምሽ በሚጠራበት መታሰቢያሽ በሚደረግበት ሁሉ በዚያ ረድኤት በረከት ይበዛል። አንቺን ያከበረውን አከብረዋለሁ። ከርስትሺም አስገባዋለሁ።" ብሏት ጌታችን ዐረገ።

ወታደሮቹ አንገቷን በሰየፉ ጊዜ ታላቅ መነዋወጽ ሆነ። ድውያን ተፈወሱ፣ ዕውሮች አዩ፣ አንካሶች ረቱ፣ የማይሰሙትም ሰሙ። ቅዱሳን መላእክትም ከሰማያት ወርደው የቅድስት መሪናን ነፍስ በዝማሬ አሳረጉ።

<3 ቅዱስ ለንጊኖስ ሰማዕት <3

ለንጊኖስ ማለት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከት ዘመን የጲላጦስ ወታደር የነበረ ሰው ነው። ስለ ጌታችን ተአምራት በየጊዜው ይሰማ ነበር። ሔዶ እንዳያገኘው ግን አይሁድን ይፈራ ነበር። እነርሱ "በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ከምኩራብ ይባረር።" ብለው ነበርና።
(ዮሐ. ፱፥፳፪)

ጌታችን በተሰቀለባት ዕለተ ዓርብ ግን ጭንቅ ሆነበት። ጌታን እንዲሰቅሉ ከታዘዙ ወታደሮች እንደ አንዱ ተመርጦ ነበርና በዘዴ አሞኛል ብሎ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ቆየ።

በኋላ ግን አይሁድ "በክርስቶስ ሞት ያልተባበረ ሁሉ ወንጀለኛ ነው።" የሚል አዋጅ በማስነገራቸው እየፈራ ወደ ቀራንዮ ሲደርስ "ጐኑን ውጋው።" ብለው ረዥምና ጥቁር ጦር ሰጡት። ለንጊኖስ ወደ ጌታችን ዓይን ተመለከተ። እያየው እንዳልሆነ ገመተ።

ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በባሕርይ ሥልጣኑ ለይቷልና ጦሩን ጨብጦ ወደ ጌታ ጐን ልኮ ወጋው። ከጌታ ቀኝ ጐንም በ"ለ" አምሳል ትኩስ ደምና ውኃ ፈሰሰ። አንዷ ፍንጣቂ ሔዳ የታወረች ዓይኑ ላይ ዐርፋ ዓይኑን አበራች።

ለለንጊኖስ ታላቅ ደስታ ሆነ። ለእኛ ግን ማየ ገቦና ደመ ገቦ ፈለቀልን። የጌታችን ትእግስቱና ቸርነቱ ግን ይደንቃል።
"ከመ ኢየሐስብ ቦቱ ዘኩናተ እዱ ርግዘቶ
በኃጣውኢሁ ለዘኢፈቀደ ሞቶ
ምሕረቶ እሴብሕ ወዐዲ ትዕግስቶ።" እንዳሉ ሊቃውንት።

ጌታችን ከተነሣ በኋላ ለንጊኖስ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘንድ ሒዶ ስለ እውነት ስለ ሃይማኖትም ተማረ። ተጠምቆ ምድራዊ ወታደርነቱን ትቶ እየሰበከ ከኢየሩሳሌም ወደ ቀጰዶቅያ ወረደ። ለዘመናትም ጌታችን ክርስቶስን በሥርዓተ ወንጌል አገለገለ።

በመጨረሻም በጢባርዮስ ቄሣር ዘመን አይሁድ አሳደዱት፤ አንገላቱት። የእነርሱ ወገን ስለነበረም መከራ አጸኑበት። የጽድቅ አርበኛና የክርስቶስ ሐዋርያ ቅዱስ ለንጊኖስ ግን ጸና። በዚህች ዕለትም አይሁድ አንገቱን ቆርጠውት ለሰማዕትነት በቃ። ቅዱሱ በሕይወቱም በዕረፍቱም ተአምራትን ሠርቷል።

እግዚአብሔር በቸር ጥሪው ሁላችንም ወደ ቀናው የጽድቅ ጐዳና ይጥራን። ከሰማዕታቱም ረድኤት በረከት ይክፈለን።

ሐምሌ ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት መሪና እናታችን (ታላቋ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ለንጊኖስ ሐራ (ሐዋርያና ሰማዕት)
፫.ቅዱስ አብጥልማዎስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እስራኤል)
፬.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮.አባ ሳሙኤል
፯.አባ ስምዖን
፰.አባ ገብርኤል

"ወደ ጌታ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም። ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጐኑን በጦር ወጋው። ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ። ያየውም መስክሯል ምስክሩም እውነት ነው። እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል። ይህ የሆነ "ከእርሱ አጥንት አይሰበርም።" የሚል የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። ደግሞም ሌላው መጽሐፍ "የወጉትን ያዩታል።" ይላል።"
(ዮሐ ፲፱፥፴፫-፴፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሰማዕታት አበው አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊ፣ ቅዱስ መቃርስ እና ቅዱስ ለውንትዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ <3

ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ምንም እንኳ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው ያን ያህል ዋጋ ቢከፍሉም ትውልዱም፣ መንግሥቱም፣ ራሷ ቤተ ክርስቲያናችንም ተገቢውን ክብር ሰጥተው እያሰቧቸው አይደለም። እስኪ እንዲያው ቢያንስ እንደ ክርስቲያን አንድም እንደ ኢትዮጵያዊ እነዚህ ነገሮቻቸውን እናስብ።

ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከልጅነታቸው ጀምረው ትምህርት፣ ትሕርምትና ደግነት ወዳጅ እንደ ነበሩ ይነገራል። ወቅቱ ኢትዮጵያ የራሷን ጳጳሳት የምትሻበት ጊዜ ነበርና በፈቃደ እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ የሃገራችን አራት አባቶች ጵጵስናን ተሾሙ።

እነርሱም ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስና አበው አባ ሚካኤል፣ አባ አብርሃምና አባ ይስሐቅ ናቸው። የተሾሙትም ግንቦት ፲፰ ቀን ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ነው። አቡነ ጴጥሮስ ከተሾሙ በኋላ በሐዋርያዊ አገልግሎትና በጸሎት ተግተው ኑረዋል።

በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ፋሺስት ጣልያን ሃገራችንን በወረረች ጊዜ ቆራጡ ጳጳስ በዱር በገደል ለመሔድ ተነሱ። በየበርሃው እየሔዱ አርበኞችን ሲያጽናኑ፣ ሲናዝዙ፣ ሲባርኩም ቆይተዋል። ለሃገራቸውና ለሃይማኖታቸው ረሃብ፣ ጥምና እንግልትን ታግሰዋል።

በተያዙባት በዚያች ሌሊትም በጣልያኖች ለሮም እምነትና ለአገዛዙ እንዲያጐበድዱ ተጠየቁ። ቆራጡ ሰው ግን እንቢ ቢሉ የሚደርስባቸውን እያወቁ "አይደረግም" አሉ። በማግስቱ በአደባባይ መትረየስ ተደግኖባቸው አሁንም ጥያቄ ቀረበላቸው።

አቡነ ጴጥሮስ አፋቸውን ከፍተው ሊናገሩ ጀመሩ፦ "የሃገሬ ሕዝብ ሆይ! ለሃገርህ ለሃይማኖትህ ባትጋደል ትውልድ ይፋረድህ። ለጣልያን ግን እንኳን ሰው ዛፍ ቅጠሉ መሬቱ እንዳይገዛለት አውግዣለሁ።" አሉ። በደቂቃዎች ልዩነት በግራዚያኒ ትዕዛዝ የመትረየስ ጥይት ዘነበባቸው።

አካላቸው ተበሳስቶ በሰንሰለት እንደ ታሠሩ መሬት ላይ ወደቁ። አንዱ ወታደር ቀርቦ ቢመለከት ትንሽ ትንፋሽ ነበረቻቸው። "ይሔ ቄስ አልሞተም።" ብሎ ጭንቅላታቸው ላይ ተኮሰባቸው።

አቡነ ጴጥሮስ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው ተሠው። ነገሩ በአርበኞች ዘንድ ሲሰማ ትግሉ ተቀጣጠለ። ይሄ የተደረገው ሐምሌ ፳፪ ቀን በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ነው። አቡነ ጴጥሮስም በተ/መ/ድ (UN) የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት (MARTYR OF THE MILLENIUM) በመባል ይታወቃሉ።

<3 ቅዱስ መቃርስ ሰማዕት <3

መቃርስ ማለት በልሳነ ዮናኒ ብፁዕ፣ ንዑድ፣ ክቡር ማለት ነው። ቅዱስ መቃርስ ተወልዶ ያደገው በአንጾኪያ (ሶርያ) በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን የታላቁ ቅዱስ ፋሲለደስና የቅድስት ሶፍያ ልጅ ነው። ምንም በቤተ መንግሥት ውስጥ ቢያድግም ከወላጆቹ ፍቅረ ክርስቶስን፣ ንጽሕናንና ደግነትን ወርሷል።

በተለይ ነዳያንን ሰብስቦ ዕለት ዕለት ያበላ ነበር። ቅዱሱ ያ የመከራ ዘመን ሲመጣ ሁሉም ቤተሰብ ስለ ክርስቶስ መሞትን በመምረጡ እርሱም ደስ እያለው የመከራው ተካፋይ ሆኗል።

ያን የመሰለ የቤተ መንግሥት ክብር ስለ ክርስትና ናቀው። ተገረፈ፣ ተሰቃየ፣ በእሳትም ተቃጠለ። አንድ ጊዜም በአደባባይ የሞተ ሰው በጸሎቱ አስነስቶ "መስክር" አለው። ከሞት የተነሣውም የክርስቶስን አምላክነት በመመስከሩ በአደባባይ የነበሩ ብዙ አሕዛብ በክርስትና አምነው ተሰይፈዋል።

ቅዱስ መቃርስን ግን ብዙ አሰቃይተው በዚህች ቀን አንገቱን ቆርጠውታል። ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አጽሙን አፍልሶ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጾለታል።

<3 ቅዱስ ለውንትዮስ ሰማዕት <3

ቅዱሱ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን ሃገሩ ጠራብሎስ ትባላለች። በወቅቱ በወታደርነት ነገሥታቱን ያገለግል ነበር። ድንግል፣ ደም ግባት የሞላለት ወጣት ስለ ነበር በሰዎች ፊት ሞገስ ነበረው።

እርሱ ግን ምንም ወታደር ቢሆን ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር። በተለይ ደግሞ የዳዊትን መዝሙር እየመላለሰ ይጸልየው ይወደው ነበር። ንግግሩ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ጨውነት የታሸ ነውና ብዙ ጓደኞቹን ከክህደት ወደ ሃይማኖት ከክፋት ወደ ደግነት መልሷል።

የመከራ ዘመን በደረሰ ጊዜም በገሃድ ስመ ክርስቶስን ይሰብክ ነበር። ክፉ ሰዎች ከሰውት በመኮንኑ ፊት በቀረበ ጊዜም አልፈራም። ወታደሮቹ መሬት ላይ ጥለው እየደበደቡት ደሙ እንደ ጐርፍ እየተቀዳ እርሱ ግን ይዘምር ነበር።

በመጨረሻም ስለ ክርስቶስ ፍቅር በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፏል። ቅዱስ ለውንትዮስ እጅግ ተአምረኛ ሰማዕት ነውና በእምነት እንጥራው።

እግዚአብሔር ዐጽመ ሰማዕታትን ይጠብቅልን:: ከሰማዕታቱ ጽናትን ጸጋ በረከትን ይክፈለን።

ሐምሌ ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት (ኢትዮጵያዊ)
፪.ቅዱስ መቃርስ ሰማዕት (የፋሲለደስ ልጅ)
፫.ቅዱስ ለውንትዮስ (ክቡር ሰማዕት)
፬.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት (ቅዳሴ ቤታቸው)
፭.ቅዱስ መርካሎስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፬.አባ ጳውሊ የዋህ

"እንግዲህ አትፍሯቸው። የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅም የተሠወረ ምንም የለምና። በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ። በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ። ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ። ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።"
(ማቴ ፲፥፳፮-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ለታላቁ ሰማዕት ማር ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም <3

ለስም አጠራሯ ክብር ይሁንና እመ ብርሃን ድንግል ማርያም በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታለች። በዓሉ ከሠላሳ ሦስቱ የእመቤታችን በዓላት እንደ አንዱ አይቆጠርም። ምክንያቱም ቅዱሳን ሊቃውንት በዓታ ከበዓታ ጋር ይስማማል ብለው የታኅሣሥ ሦስትን በዓል ከሠላሳ ሦስቱ ደምረውታል።

እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችው ሁለት ጊዜ ሲሆን፦
፩.ዛሬ የምናከብረውና በተወለደች በሰማንያ ቀኗ የገባችበት ነው።
(ከግንቦት ፩ ጀምረን እናስላው ሰማንያ ቀን ይመጣል።)
ኦሪት እንዳዘዘው ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና ንጽሕት ሕፃን ድንግል ማርያምን ታቅፈው የርግብ ልጆች (ግልገሎች) ዋኖስም ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሒደዋል።
ካህናቱ ዘካርያስና ስምዖን ወጥተው በደስታ ተቀብለዋቸዋል። እመቤታችን ለወላጆቿ ማኅጸን የከፈተች በኩር ናትና በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋታል።

፪.ከሦስት ዓመታት በኋላ እንደ ስዕለታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው ለእግዚአብሔር ሰጥተዋት ተመልሰዋል።

እግዚአብሔር ዛሬ ያልቃል ነገ ይደቃል የማይባለውን የድንግል እናቱን ፍቅር አብዝቶ ያድለን። በረከቷም በእኛ ላይ ጸንቶ ይኑር።

<3 ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት <3

በቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ የሆነው ማር ቴዎድሮስ የተወለደው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። አባቱ ዮሐንስ በትውልድ ግብጻዊ የሆነ ክርስቲያን ነው። እናቱ ግን አስቸጋሪና ጣዖት አምላኪ ሶርያዊት ነበረች።

ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስት ባሏ ክርስቲያን መሆኑን አታውቅም ነበር። ቴዎድሮስ (የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው።) በተወለደ ጊዜ ግን ጠብ ተነሣ። እርሱ ክርስትና ለማስነሳት ሚስት ደግሞ ወደ ጣዖት ቤት ለመውሰድ ተጋጩ። ሚስት ወገኖቿ ባለሥልጣኖች ናቸውና ልጁን ቀምታ ባሏን ዮሐንስን ወደ ግብጽ አሳደደችው።

ዮሐንስ በስደት ባለበት ሃገር ስለ ልጁ ፈጽሞ ይጸልይ ያለቅስም ገባ። እግዚአብሔር ደግሞ ልመናውን ሰማ። ማር ቴዎድሮስ ወጣት በሆነ ጊዜ ማንም ሳይጠራው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተማረ፤ ተጠመቀ። ዕለት ዕለትም ጾምና ጸሎትን ከምጽዋት ጋር ያበዛ ድንግልናውን ለመጠበቅ ይተጋ ነበር።

በዚያው ልክ ደግሞ ገና በሃያ ዓመቱ በጉልበቱ ኃያል፣ በውበቱም ደመ ግቡ፣ በጠባዩም ገራገር ነበርና ተወዳጅ ነበር። ነገሥታቱም የአንጾኪያ የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ሾሙት። እነሆ እስከ ዛሬ "የሠራዊት አለቃ" ተብሎ ይጠራል።

ማር ቴዎድሮስ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም። ይልቁኑ የነገሥታቱን (የጠላት) ልጆች በመማረክ ነው የሚታወቀው። እንዲያውም አንድ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በተደረገ ጦርነት ብቻውን አሸንፏቸዋል።

የፋርስ ሰዎች ሊዋጉ ሲመጡ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ሰይፍ ሰጠው። ፋርሶችን "በከንቱ ከምትጠፉ ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ።" አላቸው። እነርሱ ግን ተሳለቁበት። ከፈረሱ ወርዶ ወደ ምሥራቅ ዙሮ ጸልዮ በመስቀል አማተበ። በመካከላቸው ገብቶም በመልአኩ ሰይፍ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር አጠፋቸው።

አንድ ቀን ወደ አንድ ከተማ ቢገባ ዘንዶ ሲመለክ አገኘ። ይባስ ብሎ የአንዲት ክርስቲያን ልጆችን ለመስዋዕትነት ሲያቀርቧቸው ተመለከተ። በስመ ሥላሴ አማትቦ በፈረሱ ላይም ተቀምጦ ዘንዶውን በጦር ገደለው። የዘንዶውም ርዝመት ሃያ አራት ክንድ ነበር።

ከነገር ሁሉ በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ስለ አባቱ ወሬ ሰምቶ ካለበት ሥፍራ አፈላልጎ አግኝቶ ደስ አሰኘው። እስኪያርፍ አብሮት ቆይቶ ቀብሮት ወደ አንጾኪያ ሲመለስ ግን የሚያሳዝን ነገር ጠበቀው።
ክርስቶስ ተክዶ፣
ጣዖት ቁሞ፣
አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው፣
የክርስቲያኖች ደም ፈሶ፣
ከተማዋ በግፍ ተሞልታ ተመለከተ። እርሱም በዚያች ሰዓት መወሰን ነበረበትና አደረገው። የሁሉ ሠራዊት አለቃ ቢሆንም የክብር ልብሱን አውልቆ ባጭር ታጥቆ በንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ፊት ቆመ።

ማር ቴዎድሮስ በአደባባይ እንዲህ ተናገረ፦ "አንሰ አመልኮ ለክርስቶስ ንጉሠ ስብሐት በኩሉ ልብየ ወእሠውዕ ሎቱ - እኔስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን በፍጹም ልቤ አመልከዋለሁ። ለእርሱም ብቻ እሠዋለሁ።" ንጉሡ በቁጣ መሬት ላይ ጥለው እንዲደበድቡት አዘዘ። ወታደሮቹ ደሙ እስኪንጠፈጠፍ ገረፉት።

በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃይተው በእሳት አቃጠሉት። እርሱ ግን በጸሎቱ እሳቱን ውኃ አደረገው። ወታደሮቹ እርሱን በብዙ አሰቃዩ። እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ጸና ታገሠ።

በመጨረሻም ጌታችን በግርማ ወርዶ "ወዳጄ ቴዎድሮስ ስምህን የጠራ፣ መታሠቢያህን ያደረገ፣ ገድልህን (ዜናህን) የጻፈ፣ ያጻፈ፣ ያነበበ፣ ገዝቶ በቤቱ ውስጥ ያኖረውን ሁሉ እምርልሃለሁ።" አለው።

በስሙም ረድኤት እንደሚደረግ ነግሮት ዐረገ። ወታደሮቹም በዚህች ቀን አንገቱን ሰይፈው የክብር አክሊልን ተቀብሏል። እጅግ ብዙ ሺህ ሰዎችም አብረውት ተሰይፈዋል።

ቸሩ ፈጣሪ ከሰማዕቱ በረከት ይክፈለን።

ሐምሌ ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም (በሰማንያ ዕለት)
፪.ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት (የሠራዊት አለቃ)
፫.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘእስክንድርያ
፬.አራት መቶ አራት ሰማዕታት (የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበር)
፭.ቅድስት አውስያ (የማር ቴዎድሮስ እናት - በልጇ ምክንያት ያመነች እናት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፪.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፫.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፬.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፭.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

"እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን።"
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. ፸፫)

"በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ፤ አትናወጡም። ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን።"
(፩ጴጥ ፫፥፲፫-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳኑ ገብርኤል ሊቀ መላእክት፣ ቂርቆስ ወኢየሉጣ፣ በጥላን ጠቢብና ሰማዕታተ እስና ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ ወቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት <3

ቅድስት ኢየሉጣ እናታችን በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩና በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳት አንዷ ናት። በወቅቱ ቅዱስ ቂርቆስ የሚባል ደግ ልጅ ወልዳ ባሏ ባለመኖሩ በመበለትነት ትኖር ነበር። የዚያ ዘመን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ የነበራቸው ፍቅር ከመነገር በላይ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ መከራው በጸጉራቸው ቁጥር ልክ ነበር።

ከሮም ግዛት በአንዱ ከቅዱስ ልጇ ጋር የምትኖረው ቅድስት ኢየሉጣ የስደቱ ዘመን ሲመጣ እርሷም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ተሰደደች። እስክንድሮስ የተባለው ከሃዲ ንጉሥ ግን ያለችበት ድረስ ተከትሎ እንድትያዝና እንድትቀርብ አደረገ።

ወዲያውም "ስምሽ ማን ይባላል?" ቢላት "ክርስቲያን እባላለሁ።" አለችው። ንጉሡ ተቆጣ። "መዋቲ ስሜን ከፈለክ ኢየሉጣ ይባላል።" አለችው። ንጉሡ መልሶ "አሁን ለጣዖት ካልሠዋሽ ሲጀመር ስቃይ ቀጥሎም ሞት ይጠብቅሻል።" ቢላት ቅድስቲቱ መልሳ "በከተማ ውስጥ የሦስት ዓመት ሕፃን አለና እርሱን አምጣው። ማንን ማምለክ እንዳለብን ይነግረናል።" አለችው።

አስፈልጐ ቅዱስ ቂርቆስን አስመጣው። "ስምህ ማን ይባላል?" አለ ንጉሡ። "ከማይደፈርስ ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ጥሩ ምንጭ ስሜ ክርስቲያን ይባላል። መዋቲ ስሜን ከፈለግህ ግን ቂርቆስ ይባላል።" አለው።

ንጉሡ ሊያታልለው "ደስ የተሰኘህ ሕፃን" ቢለው ቅዱሱ ሕፃን "ትክክል ተናገርክ ለእኔ በሰማያት ደስታ ይጠብቀኛል። አንተ ግን እውነተኛው አምላክ ይፈርድብሃል።" አለው። በሦስት ዓመት ሕፃን አንደበት ዘለፋ የገጠመው ከሃዲ ተቆጣ።
እናትና ልጅን በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃያቸው።

ሰውነታቸውን ቸነከረ፣ አካላቸውን ቆራረጠ፣ ዓይናቸውን አወጣ። ሌላም ሊናገሩት የሚጨንቅ ስቃይን አሰቃያቸው። በዚህች ቀን ግን ትልቅ ድስት አሰርቶ ባሩድ፣ አረር፣ ስብና የመሳሰሉትን ጨምረውበት በእሳት አፈሉት።

የእሳቱ ወላፈን አካባቢውን በላው። በድስቱ ውስጥ ያለው ነገር እየፈላ ሲገላበጥ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ይጮህ ነበር። የስድስት ሰዓት የእግር መንገድ ድረስም ተሰምቷል። ቅድስት ኢየሉጣ ይሔኔ ነበር ልቧ ድንግጥ ያለው። ሕፃኑ ቂርቆስ የእናቱን ፍርሃት ሲመለከት ጸለየ።

"ፈጣሪዬ! ፍሬው ያለ ግንዱ አይቆምምና እኔን እንዳጸናህ እናቴንም አጽናት።" ሲል ለመነ።
"እግዚኦ ትፈቅድኑ ለፍሬሁ ተአልዶ
እንዘ በእሳት ታውኢ ጉንዶ" እንዲል።
በዚያች ሰዓት ቅድስት ኢየሉጣ ዓይኖቿ ተከፍተው ሰማያዊ ክብርን ተመለከቱና ልቧ ወደ ድፍረቱ ተመለሰ።

ልጇንም "አንተ አባቴ ነህ፤ አንተን የተሸከመች ማኅጸኔ የተባረከች ናት።" አለችው። ከዚያም ሁለቱንም ወደ ፈላው ድስት ውስጥ ቢጨምሯቸው ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደላቸው። በበትረ መስቀሉ ባርኮ የፈላውን አቀዘቀዘው። የነደደውን ውኃ አደረገው። ቅዱሳኑ ቂርቆስና ኢየሉጣ ከብዙ መከራ በኋላ በሰማዕትነት አልፈዋል።

<3 ቅዱስ በጥላን ጠቢብ <3

ቅዱሱ ከአሕዛብ ወላጆቹ ተወልዶ ያደገውም በጣዖት አምልኮ ነው። በሙያው እጅግ የተመሠከረለት ሐኪም ነበር። የሃገሩ ሰዎች "ጠቢብ" እያሉም ይጠሩታል። በጥላን ምንም ጣዖት አምላኪ ቢሆን በተፈጥሮው ተመራማሪና ቅን ነበር።

አንድ ካህንም በጐረቤቱ ነበርና ዘወትር ስለ ሃይማኖት ይከራከሩ ነበር። ካህኑ ሌሊት ሌሊት ስለ በጥላን ተግቶ ይጸልይ ነበርና ተሳክቶለት አሳመነው።

አንድ ቀን በጥላን መንገድ ሲሔድ እባብ ሰው ነድፎ ለሞት ደርሶ አየውና ጸሎት አድርሶ ስመ ክርስቶስን ቢጠራ የተነደፈው ድኖ እባቡ ሞተ።

በዚህ ተዓምር ደስ ብሎት ወደ ካህኑ ሒዶ ተጠመቀ። ከዚያም ጾም ጸሎትን ጀመረ። በየቦታው እየዞረ ሕሙማንን እንደ ቀድሞው በመድኃኒት ሳይሆን በጸሎት ያድናቸው ነበር። ስላዳናቸውም በርካቶቹ ወደ ክርስትና መጡ።

የአካባቢው ሰው ወላጆቹን ጨምሮ ክርስቲያኖች ሆኑ። በመጨረሻም ቅዱስ በጥላን፣ ቤተሰቦቹ፣ ካህኑና ከደዌ የዳኑት ወገኖቹ በአካባቢው ጣዖት አምላኪ ንጉሥ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ሰብከው በሰማዕትነት ዐርፈዋል።

<3 ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና <3

እስና ማለት ግብጽ ውስጥ የምትገኝ የቀድሞ አውራጃ ናት። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በከተማዋ በርካታ ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር። የእንዴናው መኮንን መጥቶ "ክርስቶስን ካዱ፤ ለጣዖት ስገዱ።" አላቸው። ሕዝቡ በአንድ ድምጽ መለሱ፦ "ይህማ ፈጽሞ ሊደረግ አይችልም።" መኮንኑ ተቆጥቶ "ሁሉንም ግደሉ።" አለ።

ወታደሮቹ ሰው አልመረጡም። ከታዘለ ሕፃን አልጋ ላይ እስካለ ሽማግሌ፣ ከጤነኛ እስከ ሕመምተኛ ሁሉንም ጨፈጨፏቸው። ከተማዋ በደም ተነከረች። ከከተማዋ ክርስቲያኖች ወሬ ለመንገር አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም። ሁሉም ስለ ክርስትና ደማቸውን አፈሰሱ።

ጌታችን ስለ ሰማዕታቱ ብሎ ደማቸውንም አስቦ በሃይማኖታችን ያጽናን። ከመከራም ይሰውረን። በረከታቸውንም ያድለን።

ሐምሌ ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ቂርቆስ ወእሙ ኢየሉጣ
፫.ቅዱስ በጥላን ጠቢብ ሰማዕት እና ማኅበሩ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፪.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፫.አቡነ ስነ ኢየሱስ
፬.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ መራቆት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቆጠርን።' ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ ፰፥፴፭-፴፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለነቢዩ ቅዱስ ዮናስ እና ለእናታችን ቅድስት አውፎምያ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዮናስ ነቢይ <3

በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዮናስ ከክርስቶስ ልደት ስምንት መቶ ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ይታመናል። ሊቃውንት እንዳስተማሩን ደግሞ እናቱ ቅዱስ ኤልያስን የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ናት። ቅዱስ ዮናስ ገና ሕፃን ሳለ በእስራኤል ምድር ዝናብ ለሦስት ዓመታት ከስድስት ወራት ተከልክሎ ነበር።

ይህንንም ያደረገው ደጉ ነቢይ ኤልያስ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ ነው። በወቅቱ ኤልያስ በሰራፕታ ሳለ ሕፃኑ ዮናስ ታሞ ሞተ። ልጇ የሞተባት መበለትም ኤልያስን ለመነችው። ኤልያስም ወደ ፈጣሪው ማልዶ ሕፃኑን ዮናስን ከሞት አስነስቶታል። ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከጓደኞቹ (ከነቢያቱ) አብድዩና ኤልሳዕ ጋር ሆነው ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ተከትለውታል።

ኤልያስ ካረገ በኋላ ሁሉም በየተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተዋል። ቅዱስ ዮናስን እግዚአብሔር "ወደ ነነዌ ሒደህ ንስሐን ስበክ።" አለው። ዮናስ ግን የፈጣሪውን መሐሪነት ጠንቅቆ ያውቃልና አልሔድም አለ። (ተመልከቱ የየዋሕነት ብዛት)

እግዚአብሔር እየደጋገመ እንዲሔድ ሲነግረው ነቢዩ "እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል።" ብሎ ሊኮበልል ወጣ። ነገር ግን አልቀናውም። በእርሱ ምክንያት ማዕበል ተነሣ። ሕዝቡም ሊያልቁ ሆነ። ከእንቅልፉ የነቃው ዮናስ ከመርከቡ ላሉት አሕዛብ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሰብኮላቸው በእርሱ ጠያቂነት ሐምሌ ፲፭ ቀን ወደ ባሕር ጥለውታል።

ዓሣ አንበሪም ተቀብሎታል። በግዙፉ ዓሣ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም፣ በጸሎትና በምስጋና ለሦስት ቀን ቆይቷል። ሙስና ሳያገኘውም በዚህች ቀን ዓሣ አንበሪው ነነዌ ዳር ላይ ተፍቶታል። ቅዱስ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዓባይ ሃገር - እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች።" ብሎ አሰምቶ ሰበከ።
ዮናስ ፫፥፬

የነነዌ ሰዎችም በስብከተ ዮናስ አምነው ንስሐም ገብተው ድነዋል። በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ አመስግኗቸዋል። ቅዱስ ዮናስ መኮብለሉ በሐዲስ ኪዳን ለሚደረገው ምሥጢረ ትንሣኤ ጥላ (ምሳሌ) ነውና ይደነቃል።
(ማቴ. ፲፪፥፴፰)
ነቢዩ ግን በተረፈ ሕይወቱ ሕዝቡን ሲያስተምር ፈጣሪውን ሲያገለግል ኑሮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።

<3 ቅድስት አውፎምያ ሰማዕት <3

እናታችን ቅድስት አውፎምያ (ስሟ አፎምያ አይደለም። በስሕተት "ው" መካከል ላይ የገባች እንዳይመስልዎ። እስመ ከመዝ ስማ - ስሟ እንዲሁ ነው የሚጠራው።) በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩ ወጣት ክርስቲያኖች አንዷ ናት። ገና ከልጅነቷ ልቧ በፍቅረ ክርስቶስ የተነደፈ ነበር።

በዚህም ምክንያት ራሷን በጾምና በጸሎት ወስና ትኖር ነበር። እድሜዋ ገና በአሥራዎቹ ቢሆንም በመንኖ ጥሪት መኖር ምርጫዋ ነበር። ሊቃውንት አበው ከሰማዕትነቷ ደርበው "ጻድቅት አውፎምያ" እያሉም ይጠሯታል።

አንድ ቀን ግን መንገድ ወጥታ ነበርና ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ተመለከተች። ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ሞት ተፈርዶባቸው ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር። አሕዛብ ግብራቸው የአውሬ ነውና ርኅራኄ የላቸውም። ሰማዕታቱ ደማቸው በየመንገዱ እየፈሰሰ ጥቁር ሰንሰለት በአንገታቸው፣ በእጃቸውና በእግራቸው ላይ አድርገው ይጐትቷቸው ነበር።

ቅድስት አውፎምያ የተደረገውን ሁሉ ተመልክታ አምርራ አለቀሰች። ፈጠን ብላም ወደ መኮንኑ ቀርባ ገሰጸችው። "አንተ አእምሮ የጎደለህ! እንዴት ክርስቲያኖችን እንዲህ ታሰቃያለህ? አምላካቸው ጌታ ክርስቶስ ታጋሽ ባይሆን ኑሮ በቅጽበት ከገጸ ምድር ባጠፋህ ነበር።" አለችው።

በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑ "አንቺስ ማንን ታመልኪያለሽ?" ሲል ጠየቃት። እርሷም "ሰማይና ምድርን የፈጠረውን ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አንባ የተሠዋውን ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ።" ስትል መለሰችለት። በዚያች ሰዓት የመኮንኑ ቁጣ በቅድስቷ ላይ ነደደ።

ነገር ግን ቁጣውን ከቁም ነገር አልቆጠረችውምና እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ። ወታደሮቹ ሥጋዋን በብዙ አሰቃዩ። ብላቴናዋ አውፎምያ ግን ጽንዕት ናትና አልቻሏትም። በመጨረሻ በእሳት ተቃጥላ ትሞት ዘንድ ተፈረደባት።

እሳቱ ከመሬት ከፍ ባለ ጊዜ ወደ ውስጥ ወረወሯት። በእሳቱ መካከል ቁማ ለረዥም ጊዜ ጸለየች። ከዚያም ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች። ምዕመናን በክብር ገንዘው ቀብረዋታል።

አምላካችን ከነቢዩና ከሰማዕቷ ወዳጆቹ በረከት ይክፈለን።

ሐምሌ ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ (ከዓሣ አንበሪ ሆድ የወጣበት)
፪.ቅድስት አውፎምያ (ጻድቅትና ሰማዕት)
፫.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት (ታላቁ)
፬.ቅዱስ ዘካርያስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
፫.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬.አባ ገሪማ ዘመደራ
፭.አባ ጰላሞን ፈላሢ
፮.አባ ለትጹን የዋህ
፯.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆጵሮስ)

"በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና 'መምህር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን።' አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው 'ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል። ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል። በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና። እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።"
(ማቴ ፲፪፥፴፰-፵፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለማሪ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እና ለብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ <3

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ፪፻፺፰ (፫፻፮) ዓ.ም ነው። ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ። (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም።)

ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር። የሰማዕትነት፣ የሐዋርያነት፣ የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው። ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ።

ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምህርት ነው። የሚገርመው መምህሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይህንኑ አጥብቆ አስተምሮታል።

ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር። ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና። እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት ይገዛላትም ገባ።

እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር። እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን(ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር።

በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ፫፻፲፯ (፫፻፳፭) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምህረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምህርትና በረከትን አግኝቷል።

ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራእይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይህማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው።" አለው። እርሱም መምህሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ። ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል።

በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል። ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር። ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር። "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ እንደ እንጀራ ተመግቤው፣ እንደ ውኃ ጠጥቼው፣ እንደ ልብስም ተጐናጽፌው" እያለ ይመኝ ነበር።

አፍጣኒተ ረድኤት ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት። ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት። ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ በፊቱም ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ፣ በፊቷ ቆሞ፣ በመንፈስ ቅዱስም ተቃኝቶ ነው።

ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች። ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል። ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው።

እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ" ብሎ ጸልዩዋል። "የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ።" እንደ ማለት ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ ተክሪት በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል።

በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል። የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል። ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል። በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል። ተአምራትንም ሠርቷል። በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ፫፻፷፭ (፫፻፸፫) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል።

ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል።
ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን፦
፩.ቅዱስ ኤፍሬም
፪.ማሪ ኤፍሬም
፫.አፈ በረከት ኤፍሬም
፬.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም
፭.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም
፮.አበ ምዕመናን ኤፍሬም
፯.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም አባታችን አንተ ነህ።

ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን፣ ክብሩን፣ አእምሮውን፣ ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን፤ አሳድሪብን። አሜን።

<3 ጴጥሮስ ወጳውሎስ <3

ዳግመኛ በዚህች ቀን ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ይታሠባሉ።
ቅዱሳኑ ሶርያ አካባቢ ውስጥ ወደምትገኝ አንዲት ሃገር ገብተው ሕዝቡን ከንጉሣቸው ጰራግሞስ ጋር አሳምነው አጥምቀዋል። ነገር ግን እነርሱ ሲወጡ ሰይጣን አስቶት አጥፊ ሰው ወደ መሆን ተመልሶ ንጉሡ ሐዋርያትን አሰቃይቷቸዋል።

ስለ ቅዱሳኑ ግን ፈረሶቹ ሰግደው በሰው አንደበት ቅድስናቸውን መስክረዋል። በመጨረሻም ንጉሡን ከነ ሕዝቡና ሠራዊቱ በዓየር ላይ ሰቅለው ንስሐ ሰጥተውታል። በእነዚህ ተአምራትም ሁሉም አምነው ለከተማዋና ለሕዝቡ ድኅነት ተደርጓል።

ከአባቶቻችን አበው ሐዋርያት በረከት ይክፈለን።

ሐምሌ ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፪.ብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስ ወጳውሎስ
፫.አባ ሓርዮንና ደቀ መዛሙርቱ (ሰማዕታት)
፬.አባ ፍሬምናጦስ መስተጋድል

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት
፫.ቅድስት እንባ መሪና
፬.ቅድስት ክርስጢና

"ለምኑ ይሰጣችሁማል። ፈልጉ ታገኙማላችሁ። መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና። የሚፈልገውም ያገኛል። መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል።"
(ማቴ ፯፥፯-፰)

"የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል።
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፴-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ብስንድዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ብስንድዮስ ጻድቅ <3

ቅዱስ ብስንድዮስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ድንቅ ሥራ ከሠሩት እንደ አንዱ ሆኖ ይዘከራል። ቅዱሱ ግብጻዊ ሲሆን በልጅነቱ ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል። የሚገርመው የብሉይም ሆነ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ ያጠናቸው በቃሉ ነበር።

በእርግጥ ይህንን ማድረግ የቻሉ በርካታ የሃገራችን ሊቃውንት ዘንድሮም አሉ። ልዩነቱ ግን ወዲህ ነው። ቅዱስ ብስንድዮስ መጻሕፍቱን ያጠናቸው ለሕይወት እንጂ ለእውቀት አልነበረምና ሁሌም ነግቶ እስከሚመሽ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እያጣጣመ ይጸልይ ነበር። ይህንን ሲያደርግ ደግሞ ባጭር ታጥቆ ጫማውን አውልቆ በባዶ ሆዱ ቁሞ ነው።

ታዲያ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ክፍል ሲጸልይ ነቢይ ቢሆን ሐዋርያ ወደ እርሱ ይወርድለት ነበር። ለምሳሌ ዘፍጥረትን ሲጸልይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ይመጣና ከፊቱ ተቀምጦ ይሰማዋል። ትንቢተ ኢሳይያስ ላይ ሲደርስ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ወንጌለ ማቴዎስ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ማቴዎስ ይመጡና ደስ እያላቸው ያደምጡት ነበር።

አንዱ ነቢይ ወይ ሐዋርያ ሲወጣ ቅዱስ ብስንድዮስን ባርኮ ሌላኛውን ተክቶ ነው። በዚህ ምክንያት የቅዱሱ ሕይወት በምድር እያለ ሰማያዊ ሆነ።
ሰማንያ አንዱን አሥራው መጻሕፍት የጻፉ ቅዱሳንን ለማየት በቃ፤ በእጆቻቸውም ተባረከ።

የቅዱስ ብስንድዮስ ቀጣይ የሕይወቱ ተግባር ብሕትውና ሆነ። ዓለምንና ግሳንግሷን ትቶም ወደ በርሃ መነነ። በአጽንዖ በዓት፣ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምትም ተጋደለ። በየደረሰበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር በእጆቹ ድንቅ ተአምር ይሠራ ነበር። ብዙ ድውያንን ፈወሰ አጋንንትንም ከአካባቢው አሳደደ።

በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ግን ስዕለት ስላለበት ሴቶችን ላለማየት ይጠነቀቅ ነበር። በሆድ ሕመም ትሰቃይ የነበረችና ጥሪቷን በመድኃኒት የጨረሰች አንዲት ሴት ስለ ቅዱሱ ዝና ትሰማለች። ችግሩ ግን እርሱ ከውዳሴ ከንቱና ከሴት የሚርቅ ነውና እንዴት ብላ ታግኘው? አንድ ቀን ከበዓቱ አካባቢ ተደብቃ ውላ ሲመጣ የልብሶቹን ዘርፍ ለመንካት በእምነት አሰበች።

ልክ ከበዓቱ ሲዘልቅ ስሉጥ(ፈጣን) ነበርና ገና እንዳያት ሩጦ አመለጣት። እንዳትከተለው ድውይ ናትና አልቻለችም። አዝና ዝቅ ስትል ግን የረገጠውን ኮቲ ተመለከተች። በፍጹም ልቧ በእምነት "የጻድቁ አምላክ ማረኝ።" ብላ ከአፈሩ ቆንጥራ በላች። ደቂቃ አልቆየችም፤ ፈጥና ከደዌዋ ዳነች። እንደ እንቦሳ እየዘለለች ወደ ከተማ ሔዳ ተአምሩን ተናገረች።

ከእነዚህ ዘመናት በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅፍጥ(Qift) በምትባል ሃገር ጵጵስናን (እረኝነትን) ተሹሟል። ወደ ከተማ ሲገባ የቀደመ ተጋድሎውን ቸል አላለም። ይልቁኑ ይተጋ ነበር እንጂ። ከብቃት መዓርግ ደርሷልና ሲቀድስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገሃድ ያየው ሠራዊተ መላእክትም ይከቡት ነበር።

ሕዝቡ ሊቆርቡ ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይታየው ነበር። የበቁትን እያቀበለ ያልበቁትን እየመከረና ንስሐ እየሰጠ ይመልሳቸዋል። እንዲህ በጽድቅ፣ በሐዋርያዊ አገልግሎትና በንጽሕና ተመላልሶ ቅዱስ ብስንድዮስ በዚህች ቀን ዐርፏል።

ቅዱስ ብስንድዮስ ካረፈ በኋላ ደቀ መዝሙሩ ከመግነዙ ጥቂት ቆርጦ አስቀርቶ ብዙ ድውያንን ፈውሶበታል።

ቸር አምላክ ለአባቶቻችን የሰጠውን ጸጋ ለእኛ ለባሮቹም አይንሳን። ከቅዱሱ በረከትም ያድለን።

ሐምሌ ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ብስንድዮስ ሊቅ ወጻድቅ
፪.ቅዱስ አሞን ሰማዕት (ዘሃገረ ጡህ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬.ቅዱስ አስከናፍር
፭.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

"አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር። ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና። ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጐ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።"
(፪ጢሞ ፫፥፲፬-፲፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ ወሰማዕት <3

ቅዱስ ዮሐንስ በቀደመው ዘመን ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ መርባስ ትባላለች። ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚወዱ፣ ምጽዋትን የሚያዘወትሩና በበጐው ጐዳና የሚኖሩ ነበሩ። ነገር ግን ልጅ በማጣታቸው ምክንያት ፈጽመው ያዝኑ ይጸልዩም ነበር። በተለይ ለመጥምቁ ዮሐንስ ልዩ ፍቅር ስለ ነበራቸው ዝክሩን ይዘክሩ በስሙም ይማጸኑ ነበርና መጥምቁ ሰማቸው።

ወደ ፈጣሪውም ልመናቸውን በማድረሱ መልክ ከደም ግባት የተባበረለት ደግ ልጅን ወለዱ። እጅጉን ደስ ስላላቸው በአካባቢያቸው የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስን ቤተ ክርስቲያን በገንዘባቸው አነጹ። ሕፃኑንም በመጥምቁ ስም "ዮሐንስ" አሉት። ጻድቁ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር አድሮበታልና ሕይወቱ ግሩም ነበር።

በሕፃን ገላው ይጾምና ይሰግድ በልጅ አንደበቱም ተግቶ ይጸልይ ነበር። ወላጆቹ ወደ እረኝነት ባሰማሩት ጊዜም መፍቀሬ ነዳያን ነውና ቁርስና ምሳውን ለነዳያን እያበላ እርሱ ጾሙን ይውል ነበር። አባቱ የሚያደርገውን ሰምቶ ለማረጋገጥ ተከተለው። እንዳሉትም እናቱ ጋግራ የሰጠችውን ትኩስ ዳቦ ለነዳያን ሲሰጥ አየው።

ሊቆጣው ፈልጐ "ዳቦህ የታለ?" ቢለው ሕፃኑ ቅዱስ ዮሐንስ "በአገልግሉ ውስጥ አለ።" ሲል መለሰለት። አባት ለመቆጣት እንዲመቸው አገልግሉን ሲከፍተው ግን ያየውን ማመን አልቻለም። በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ዳቦዎቹ ትኩስ እንደሆኑ ተገኙ።

አባትም ወደ ቤቱ ወስዶ "ልጄ! አንተ የእግዚአብሔር ሰው ስለሆንክ እኛን ሳይሆን እርሱን አገልግል።" ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላከው።

በዚህ ምክንያት ቅዱስ ዮሐንስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ትምህርት ገባ። በስድስት ዓመታትም ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ። አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላው ደግነቱን ወደዋልና በግድ ቅስና ሾሙት። እርሱ ግን ለተወሰነ ጊዜ አስተምሮ ዘመዱ የሆነውንና ዲያቆኑን ቅዱስ ስምዖንን አስከትሎ መነነ።

በዚያም በፍጹም ገድል ሲኖር ብዙ ተአምራትን ሠርቷል።
አንድ ወታደር (አንድ ዓይና ነው።) ሊባረክ ብሎ ሲጐነበስ የታወረች ዓይኑን የቅዱስ ዮሐንስ ልብስ ቢነካት በርታለታለች። ከዚህ አልፎም ቅዱሱ ብዙ ድውያንን ፈውሷል፣ ለምጻሞችን አድኗል፣ አጋንንትን ከማደሪያቸው (ከሰው ላይ) አሳድዷል።

ታዲያ አንድ ቀን የወቅቱ የአንጾኪያ ንጉሥ የቅዱስ ዮሐንስን ዜና ይሰማል። የእርሱ ልጅ ደግሞ አጋንንት አድረውባት ስቃይ ላይ ነበረችና የሚያድናት አልተገኘም። ንጉሡ "ጻድቁን አምጡልኝ።" ብሎ መልእክተኛ ሲልክ ቅዱስ ዮሐንስ ደመና ጠቅሶ በዚያውም ላይ ተጭኖ ከተፍ አለ። ንጉሡ አይቶት ደነገጠ። አባ ዮሐንስ ግን "እኔ ኃጢአተኛ የሆንኩ ሰው ለምን እንዲህ ትፈልገኛለህ?" ብሎ ታማሚዋን አስጠራ።

ጻድቁ እጆቹን አንስቶ ወደ ፈጣሪው ሲጸልይ በወጣቷ ላይ ያደረው ሰይጣን ሕዝቡ እያዩት ከሆዷ በዘንዶ አምሳል ወጥቶ ሔደ። ንጉሡ ስለተደረገለት ውለታ ለቅዱስ ዮሐንስ ወርቅና ብር ብዙ ሽልማትም አቀረበ። አባቶቻችን እንዲህ ዓይነት ነገር አይወዱምና ቅዱሱ "እንቢ አልወስድም።" አለ።

ቅዱስ ዮሐንስ "ልሒድ" ብሎ ሲነሳ ንጉሡ "አባቴ ወድጄሃለሁና አትሒድ።" ብሎ የልብሱን ዘርፍ (ጫፍ) ያዘው። በቅጽበት ግን ደመና መጥታ ነጥቃ ወሰደችው። የቀሚሱ ቁራጭም በንጉሡ እጅ ላይ ቀረች። እርሱም ቤተ ክርስቲያን አሳንጾ ያችን የተባረከች ጨርቅ በክብር አኑሯታል።

ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ስምዖን (ደቀ መዝሙሩ) ግን ከብዙ የተጋድሎ ዓመታት በኋላ ሌላ ክብር መጣላቸው። "ክርስቶስን ካዱ፤ ለጣዖት ስገዱ።" የሚል ንጉሥ በመነሳቱም ሒደው በጌታችን ስም መሰከሩ። በገድል በተቀጠቀጠ ገላቸው ላይ ግርፋትን እሳትን ታገሱ። በዚህች ቀንም አንገታቸውን ተቆርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃቸው ይማረን። ከበረከታችቸውም ያድለን።

ሐምሌ ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ዮሐንስ (ሰማዕት ወጻድቅ)
፪.ቅዱስ ስምዖን (ደቀ መዝሙሩ)
፫.አባ ኢሳይያስ ዘገዳመ አስቄጥስ
፬.አባ ገብርኤል ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፫.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
፬.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
፭.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት

"ሒዳችሁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። ድውዮችን ፈውሱ፣ ሙታንን አንሱ፣ ለምጻሞችን አንጹ፣ አጋንንትን አውጡ። በከንቱ ተቀብላችሁ በከንቱ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ። ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።"
(ማቴ ፲፥፯-፲)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ አባ ኅልያን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ኅልያን ገዳማዊ <3

ጻድቁ ተወልዶ ያደገው ዓይነ ፀሐይ በምትባል የቀድሞ የግብጽ ክፍለ ሃገር ሲሆን ወላጆቹ ዲስጣና ካልሞና ይባላሉ። እነርሱ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩና ገና በልጅነት ይህንኑ አጥብቀው አስተምረውታል። ቅዱሱ ኅልያን ጾምን፣ ጸሎትን ብቻ ያይደለ በሥጋዊ ሙያውም የተመሰገነ አንጥረኛ ነበር።

በወዙ በላቡ ሠርቶ ያገኘው ሃብት ነበረው። በተለይ ወርቅና ብር እየሠራ ይተዳደር ከገቢውም ነዳያንን ያስብ ነበር። እንዲህ ባለ ግብር ሳለ አንድ ቀን ፈተና መጣበት። አንዲት ዐረባዊት ሴት መጥታ የጆሮ ጌጥ (ጉትቻ) እንዲሠራላት ትጠይቀውና እርሱም ከወርቅ ይሠራላታል። የጆሮ ጌጡን ከሰጣት በኋላ ግን "ዋጋውን አልሠጥህም።" ትለዋለች።

እርሱም "ምነው እኅቴ! የደከምኩበትን ለምን አትከፍይኝም?" ሲላት ገላዋን አጋልጣ "ሴትነቴን ልስጥህ?" ብላ ለዝሙት ጠየቀችው። ድንግሉ ኅልያን ከአነጋገሯና ከድርጊቷ የተነሳ በጣም ደነገጠ። ከፊቷ ላይ አማትቦ ገስጿት ወደ ቤቱ ሔደ። ሙሉ ሌሊት ሲያዝን አደረ። ሊነጋጋ ሲል በልቡ ወሰነ። ይህችን ዓለም ሊተዋትም ቆረጠ።

በወጣት ጉልበቱ ደክሞ ያፈራው ሃብቱ፣ ንብረቱ፣ ቤቱ፣ መሬቱ፣ ወርቁና ብሩ አላሳሳውም። ነዳያንን ሁሉ ወደ ቤቱ ጠርቶ ሙሉ ንብረቱን አካፈላቸው። የተረፈችው የለበሳት ልብስ ብቻ ነበረችና ፈጽሞ ደስ እያለው ከተማውን ጥሎ ወደ በርሃ ተሰደደ። ልቡናን የሚመረምር ጌታ ሊመራው ወዷልና ሦስት ቅዱሳን ስውራንን ሰደደለት።

ሦስቱም የብርሃን አክሊል ደፍተው፣ የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሰው፣ የብርሃን ዘንግ ይዘው ተገለጡለት። እየመሩም ወስደው በግራና በቀኝ ውኃ ከሚፈስባት ደኗ ለዓይን ደስ ከምታሰኝ ዱር አደረሱት። አካባቢው እንኳን ሰው እንስሳትም አልነበሩበትም። ሦስቱ ቅዱሳን ከቦታዋ እንደ ገቡ በላዩዋ ላይ ዕንቁ ያለባት የብርሃን ዘንግ ሰጥተውት "ወደ ፈጣሪ እንስገድ።" አሉት።

ሰግዶ ቀና ሲል ግን ሦስቱም በአካባቢው አልነበሩም፤ ተሠውረዋልና። አባ ኅልያን ከቅዱሳኑ በመለየቱ ፈጽሞ አለቀሰ።

ተጋድሎውን ግን በጾም፣ በጸሎትና በስግደትም አጠነከረ። ቅዱሱ የሚመገበው የሚለብሰውም ቅጠል ነበር። በእርሱ ዘንድ ሌሊት የሚባል አልነበረም። ምክንያቱም ያቺ ዘንግ ሲመሽ ግሩም የሆነ ብርሃን ታወጣ ነበርና ነው።

መንገድ መሔድ በፈለገ ጊዜም ትመራው ጐዳናውንም ታሳጥርለት ነበር። እንዲህ ባለ ግብር ለበርካታ ዓመታት ከሰው ተለይቶ ኖረ። አጋንንት በተለያየ መንገድ ፈተኑት። ግን አልቻሉትም። አቅም ሲያጥራቸው ወደ ከተማ ሔደው በሰው አርአያ ሽፍቶችን አናግረው ሊያስገድሉት ሞከሩ። ነገር ግን ከፊት ለፊት እያዩት ሽፍቶቹ ሲራመዱ ቢውሉም ሊደርሱበት አልቻሉም።

እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ መንገዱን ያረዝምባቸው ነበር። በኋላ ግን ሽፍቶቹ በድካምና በውኃ ጥም ሊያልቁ ሆነ። ጻድቁ ምንም እርሱን ለመግደል ቢመጡም አዘነላቸው። ባሕሩን ያለ ታንኳ እየረገጠ ደረሰላቸው። ከዱር ፍሬ አብልቶ ንጹሕ ውኃም አጠጥቶ ሸኛቸው።

እድሜው እየገፋ ሲሔድ አንድ ቀን እነዚያ በፊት የተሠወሩት ሦስቱ ቅዱሳን እንደ ገና ተገለጡለት። በደስታ ሲጨዋወቱ አድረው ሲነጋ አባ ኅልያን ወደ ምሥራቅ ሰግዶ ዐረፈ። ሦስቱ ቅዱሳንም ሥጋውን ገንዘው በበዓቱ ቀበሩት። ዜና ሕይወቱንም ጽፈው አስቀመጡትና እንደ ገና ተሠወሩ።

የቅዱሳን አምላክ ለእኛም የአባቶችን ረድኤት ይላክልን። ከጻድቁም በረከትን ይክፈለን።

ሐምሌ ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ኅልያን ገዳማዊ
፪.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (ዘሐምስቱ አሕጉር)
፫.ቅዱስ ታውድሮስ ሰማዕት
፬.ሰማዕታት ሉክዮስና ድግናንዮስ (በንስሐ ለክብር የበቁ የጦር አለቆች)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
፫.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
፬.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
፮.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

"ጌታ ኢየሱስም 'አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር፣ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ።' አለው። ጐበዙም 'ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ። ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው?' አለው። ጌታ ኢየሱስም 'ፍጹም ልትሆን ብትወድ ሒድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ። መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ። መጥተህም ተከተለኝ።' አለው።"
(ማቴ ፲፱፥፲፰-፳፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ እና ለቅዱሳን አበው አብርሃም፣ አባ ሲኖዳ እና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤
አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሥሉስ ቅዱስ <3

በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት) በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘላለም አምላክ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው። አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነት፤ በባሕርይ፣ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው። በዚህ ጊዜ ተገኙ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም። መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና።

ርኅሩኀን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን። የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም። የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል። በቤቱም መጥተው ያድራሉ።

ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም። አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል። ሥላሴ አኀዜ ዓለም (ዓለምን በእጁ የያዘ) ነው። ነገር ግን በፍቅር ለሚሻው በፍቅር ይመጣል።

አባታችን አብርሃም በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ እናታችን ሣራ በሰማንያ ዘጠኝ ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ። አብርሃም እግራቸውን አጠበ። (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው። (ድንቅ አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው። እንደሚበሉ ሆኑለት። በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት፤ ቅድስት ሣራ ሳቀች። እንደ ዘንድሮ ወገኖቻችን የማሾፍ አይደለም። ደስታና ጉጉት የፈጠረው እንጂ። ሥላሴ "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ" ብለው ነበርና በዚህም ምክንያት ነው "ይስሐቅ" የተባለው።

ሥላሴን ያስተናገደች ድንኳን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት። በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል (አድረዋልና)።

<3 ታላቁ አባ ሲኖዳ <3

የባሕታውን ሁሉ አለቃቸው ታላቁ ቅዱስ ሲኖዳ፦
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተወለደ፣
በእናቱ ማኅጸን ሳለ መላእክት በሰይፈ እሳት ይጠብቁት የነበረ፣
የታላቅነት ትንቢት የተነገረለት፣
ገና ሳይወለድ ሥውራን አበው የሰገዱለት፣
በሕፃን ሰውነቱ ጾምና ጸሎትን የጀመረ፣
የልጅነት ቁርስና ምሳውን ለነዳያን ያካፍል የነበረ፣
በዘጠኝ ዓመቱ ወደ በርሃ የመነነና የአባ አብጐል ደቀ መዝሙር የሆነ አባት ነው።

ሲመነኩስም በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሠለስቱ ደቂቅ አስኬማ፣ የኤልያስ ቆብዕና የመጥምቁ ዮሐንስ ቅናትን (መታጠቂያ) ከያሉበት መላእክት አምጥተውለት የመነኮሰ፣
ዓለምን በሙሉ በጸሎቱ ይጠብቅ የነበረ፣
የግብጽን በርሃ በብርሃን የሞላ፣
በርካታ ድርሰቶችን የደረሰ፣
ያለ ማቋረጥ በየቀኑ ከመቶ ዓመታት በላይ ከጌታችን ክርስቶስ ጋር የተነጋገረ፣
ደመናትን ተጭኖ ይሔድ የነበረና ያለ ዕረፍት ለመቶ አሥራ አንድ ዓመታት ከሁለት ወራት ፈጣሪውን ያገለገለ አባት ነው።

በዚህም ምክንያት አንድ ቀን ገዳማውያን ሁሉ እየሰሙ እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ መጣ። "ሲኖዳ ተሠይመ አርሲመትሪዳ" (ሲኖዳ አርሲመትሪዳ ሆኗል ማለትም ለባሕታውያን ሁሉ አለቃ ሁኖ ተመርጧል ማለት ነው።)
ቅዱሱ የጌታችንን እግር እያጠበም ይጠጣ ነበር።

በዚህች ዕለት በመቶ ሃያ ዓመቱ ጌታችን ወርዶ ሲያሳርገው አቡነ ኪሮስ "ታላቅ ምሰሶ (ታላቅ ዛፍ) ወደቀ" ብለው አልቅሰዋል። ሲኖዳ ማለት "ደግ ሰው" ማለት ነው።

<3 አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ <3

ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅና ጻድቅ የተወለደው ወሎ ጋስጫ ውስጥ በ፲፫፻፶፰ ዓ.ም ነው። ከልጅነቱ ትምህርት አልገባህ ቢለውም በልቡናው ግን ቅን እና ታዛዥ ነበር። መምህሩ "ትምህርት አይገባውምና ውሰዱት።" ቢላቸው "የእግዚአብሔር ነውና ያገልግላችሁ።" ብለው መለሱት። መገፋቱን የተመለከተ አባ ጊዮርጊስ እመቤታችንን ከልቡ ይወዳት ነበረና ይማጸናት ገባ።

ቀን ቀን ገዳሙን ሲረዳ፣ እሕል ሲፈጭና ሲከካ፣ ላቡንም ሲያፈስ ውሎ ሌሊት ደግሞ ሲጸልይ ያነጋ ነበር። ድንግል እመቤታችን ጸሎቱን ሰምታለችና ቅዱስ ዑራኤልን አስከትላ መጣችለት። በንጹሐት እጆቿ ባርካው ምሥጢርንም ነገረችው። "ወነገረቶ ሐምስተ ቃላተ" እንዲል። ጽዋዐ ልቡናን አጠጥታው ተሠወረችው።

ከዚህች ሰዓት ጀምሮ አባ ጊዮርጊስ ፍጹም ተለወጠ። በጽድቁ ላይ የሊቅነትን ካባ ደረበ። ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተነትናቸው መናፍቃንንም ምላሽ ያሳጣቸው ገባ። የተረጐማቸውና ያተታቸውን ሳይጨምር አርባ አንድ ድርሰቶችን ደረሰ። (መጽሐፈ ሰዓታት፣ መጽሐፈ ምሥጢር፣ አርጋኖን፣ ኆኅተ ብርሃን፣ ውዳሴ መስቀል፣ ወዘተ የእርሱ ድርሰቶች ናቸው።)

ስለ ሃይማኖትም ጠበቃ ነበር። ስለ ቅድስናውና ውለታው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ትጠራዋለች።
፩.ሊቀ ሊቃውንት
፪.በላዔ መጻሕፍት
፫.ዓምደ ሃይማኖት
፬.ዳግማዊ ቄርሎስ
፭.ጠቢብ ወማዕምር

ጻድቁ ሊቅ በተወለደ በስልሳ ዓመቱ በ፲፬፻፲፰ ዓ.ም በዚህች ቀን ዐርፏል። አባ ጊዮርጊስ የተወለደውም ያረፈውም ሐምሌ ፯ ቀን ነው።

የሥላሴ ቸርነት፣ የአብርሃም ደግነት፣ የአበው አባ ጊዮርጊስና አባ ሲኖዳ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን።

ሐምሌ ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን አብርሃምና ሣራ (ሥላሴን ያስተናገዱ)
፪.ብሥራተ ልደተ ይስሐቅ
፫.ታላቁ አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን ሁሉ አለቃ)
፬.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ሊቀ ሊቃውንት ኢትዮጵያዊ የሃይማኖት ምሰሶ)
፭.ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ (ምጥው ለአንበሳ)
፮.አባ መቃቢስ
፯.አባ አግራጥስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፪.አባ ባውላ ገዳማዊ
፫.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

"እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ 'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ። እያበዛሁም አበዛሃለሁ።' ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ። እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በኋላ ተስፋውን አገኘ።"
(ዕብ ፮፥፲፫-፲፬)

"የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።"
(፪ቆሮ ፲፫፥፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

ፍጡር ቢከብር ከእመ ብርሃን ቀጥሎ የእነዚህን ቅዱሳን ያህል የሚከብር አይኖርም። ለቤተ ክርስቲያን ያልሆኑላት ምንም ነገር የለምና እርሷም "ብርሃኖቼ፣ ዓይኖቼ፣ ዕንቁዎቼ" ብላ ትጠራቸዋለች።

<3 ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት <3

የዮና ልጅ ስምዖን ጴጥሮስ (ኬፋ) የተባለው በጌታችን ንጹሕ አንደበት ነው። ይሔውም ዓለት (መሰረት) እንደ ማለት ነው።
በቤተ ሳይዳ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ዓሣ በማጥመድ አድጐ፣ ሚስት አግብቶ ዕድሜው ሃምሳ ስድስት ሲደርስ ነበር ጌታችን የተቀበለው። በዕድሜውም ሆነ በቅንዐቱ፣ በአስተዋይነቱም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ተብሏል። ለሐዋርያትም አለቃቸው ሆኗል።
(ማቴ. ፲፮፥፲፯ ፣ ዮሐ. ፳፩፥፲፭)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘባት ሌሊት ለሠራው ስሕተት ንስሐ ገብቶ ምሳሌም ሆኗል። ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ እረኝነቱ ሐዋርያትን ጠብቆ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሲያበቃ ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ለሁሉም ሃገረ ስብከት አካፍሏል። ምንም የእርሱ ክፍል ሮሜ ብትሆንም አርድእትን ስለ ማጽናት በሁሉም አሕጉራት ዙሯል።

በስተእርጅናው ብዙ መከራዎችን ተቀብሏል። አሕዛብ ግብራቸው እንደ እንስሳ ነውና በአባታችን ላይ ቀልደዋል። እርሱ ግን ሁሉንም ታግሷል። የቅዱሱን ታሪክ ለመናገር ከመብዛቱ የተነሳ ይከብዳልና ልቡና ያለው ሰው ሊቃውንትን ሊጠይቅ እንደሚገባ እመክራለሁ።

ቅዱስ ጴጥሮስ መልካሙን ገድል ተጋድሎ በ፷፮ ዓ.ም የኔሮን ቄሳር ወታደሮች ሲሰቅሉት ለመናቸው። "እባካችሁን? እኔ እንደ ጌታዬ ሆኜ መሰቀል አይገባኝም።" አላቸው። እነርሱም ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል። በበጐ እረኝነቱም የማታልፈውን ርስት ከነመክፈቻዋ ተቀብሏል። በሰማዕትነት ሲያርፍም ዕድሜው ወደ ሰማንያ ስምንት አካባቢ ደርሶ ነበር።

የቅዱስ ጴጥሮስ መጠሪያዎች
፩.ሊቀ ሐዋርያት
፪.ሊቀ ኖሎት (የእረኞች/ሐዋርያት/ አለቃ)
፫.መሠረተ ቤተ ክርስቲያን
፬.ኰኩሐ ሃይማኖት (የሃይማኖት ዐለት)
፭.አርሳይሮስ (የዓለም ሁሉ ፓትርያርክ)

<3 ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ <3

የቤተ ክርስቲያን መብራቷ ቅዱስ ጳውሎስን እንደ ምን ባለ ዐማርኛ እንገልጠዋለን?
ስለ እርሱ መናገርና መጻፍ የሚችልስ እንደ ምን ያለ ሰው ነው?
የዓለምን ነገር ሲጽፍ በኖረ እጄስ እንደ ምን እጽፈዋለሁ?
ይልቁኑስ የእርሱን አሥራ አራቱን መልእክታትና ግብረ ሐዋርያትን መመልከቱ ሳይሻል አይቀርም።

ቅዱስ ጳውሎስ ከነገደ ብንያም ሳውል የሚባል የጠርሴስ ሰው ሲሆን ምሑረ ኦሪት፣ ቀናተኛና ፈሪሳዊ ነበር። ጌታ በደማስቆ ጐዳና ጠርቶ በሦስት ቀናት ልዩነት ምርጥ ዕቃ አደረገው። ይህ የሆነው በ፵፪ ዓ.ም ጌታ ባረገ በስምንተኛው ዓመት ነበር። ከዚያማ ብርሃን ሆኖ አበራ። ጨው ሆኖ አጣፈጠ።

ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም ከእንግሊዝ እስከ እልዋሪቆን (የዓለም መጨረሻ) ወንጌልን ሰበከ። ስለ ወንጌል ተደበደበ፣ ታሠረ፣ በእሳት ተቃጠለ፣ በድንጋይ ተወገረ፣ በጦር ተወጋ፣ በአፍም በመጣፍም ብሎ አገለገለ። በየቦታውም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ሠራ። ለሃያ አምስት ዓመታት ቀንና ሌሊት ያለ መታከት ወንጌልን ሰበከ።

እርሱን የመሰሉ እርሱንም ያከሉ ብዙ አርድእትን አፍርቶ በ፷፯ ዓ.ም በኔሮን ቄሳር ትእዛዝ አንገቱ ተቆርጧል። ከአሥራ አራቱ መልእክታቱ ባሻገር ቅዱስ ሉቃስ ወንጌልን ሲጽፍ አግዞታል። ልክ ቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ ማርቆስን እንዳገዘው ማለት ነው።

የቅዱስ ጳውሎስ መጠሪያዎች
፩.ሳውል (ከእግዚአብሔር የተሰጠ)
፪.ልሳነ ዕፍረት (አንደበቱ እንደ ሽቱ የሚጣፍጥ)
፫.ልሳነ ክርስቶስ (የክርስቶስ አንደበቱ)
፬.ብርሃነ ዓለም
፭.ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን መቅረዝ)
፮.የአሕዛብ መምህር
፯.መራሒ (ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚመራ)
፰.አእኩዋቲ (በምስጋና የተሞላ)
፱.ንዋይ ኅሩይ (ምርጥ ዕቃ)
፲.መዶሻ (ለአጋንንትና መናፍቃን)
፲፩.መርስ (ወደብ)
፲፪.ዛኅን (ጸጥታ)
፲፫.ነቅዐ ሕይወት (የሕይወት ትምህርትን ከአንደበቱ ያፈለቀ)
፲፬.ዐዘቅተ ጥበብ (የጥበብ ምንጭ/ባሕር)
፲፭.ፈዋሴ ዱያን (ድውያንን የፈወሰ) . . .

ጌታችን እግዚአብሔር የአባቶቻችንን ብርሃን ያብራልን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ሐምሌ ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫.ቅዱሳን ሰባ ሁለቱ አርድእት (ዛሬ ሁሉም ይታሠባሉ።)
፬.ቅዱስ ሳቁኤል ሊቀ መላእክት
፭.ቅድስት መስቀል ክብራ (የቅዱስ ላሊበላ ሚስት)
፮.ቅዱሳን ዘደብረ ዓሣ
፯.ቅዱሳት አንስት (ዴውርስ፣ ቃርያ፣ አቅባማ፣ አቅረባንያና አክስቲያና - የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታዮች)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፪.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፫.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
፬.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)

"ጌታ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ "የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህንን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፤ አንተ ጴጥሮስ ነህ። በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ። የገሃነም ደጆችም አይችሏትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ። በምድር የምታሥረው ሁሉ በሰማያት የታሠረ ይሆናል። በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።"
(ማቴ ፲፮፥፲፯-፲፱)

"በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና። የምሔድበትም ጊዜ ደርሷል። መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ። ሩጫውን ጨርሻለሁ። ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ። ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል። ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል።"
(፪ጢሞ ፬፥፮-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዓምደ ሃይማኖት ቅዱስ ቄርሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ <3

ቅዱስ ቄርሎስን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን "ዓምደ ሃይማኖት- የሃይማኖት ምሰሶ" ይሉታል።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ሊቁ የተወለደው በእስክንድርያ (ግብጽ) በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። እናቱ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎፍሎስ እኅቱ ነበረችና አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወስዶ አሳድጐታል። ገና በልጅነቱ ወደ አባ ሰራብዮን ገዳም ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል። በጾም፣ በጸሎትና በትሕትና የታሸ ነውና ሲማር አንድ ጊዜ ካነበበው በሕሊናው ተስሎ ይቀር ነበር።

ቅዱስ ቴዎፍሎስ "ምዕመናንን አስተምርልኝ።" ብሎ ወደ ከተማ አመጣው። መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና ሲያስተምር ወይ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነብ ከምዕመናን ወገን ስንኳን የሚያወራና የሚንቀሳቀስ ቀርቶ የሚቀመጥም አልነበረም። ጣዕመ ስብከቱም ብዙዎችን ለወጠ።

ከዚያም በ፬፻፲፪ ዓ.ም አጎቱ የነበረው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ሲያርፍ ጳጳሳትና ሊቃውንት በአንድነት ቅዱስ ቄርሎስን መረጡ። የእስክንድርያም ሃያ አራተኛ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሾመ። በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን አበራች። በቅድስናው፣ በሊቅነቱ፣ በስብከቱ፣ በድርሰቶቹና በትጋቱ በፍጹም አገለገላት።

በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው። ትምህርቱ ክርስቶስን "ሁለት አካል፣ ባሕርይ ነው።" (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር። በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር። ምክንያቱም ጌታችንን ወደ ሁለት የከፈለው እመቤታችንን የአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው። (ላቲ ስብሐት!)

ነገሩን ቅዱስ ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም። በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ። ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው። በ፬፻፴፩ ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና ሁለት መቶ ቅዱሳን ሊቃውንት ተገኙ።

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በኋላ ጉባዔው ተጀመረ። አፈ ጉባዔው ሊቀ ማኅበር ማር (ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው። ምላሽም አሳጣው። ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን ድንግል ማርያምም ወላዲተ አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ በምሳሌም እያሳየ አስረዳ።
የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ። ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት አሥራ ሁለት አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ። እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ። ይነበባሉ፤ ይተረጎማሉ።

ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም "ታኦዶኮስ (የእግዚአብሔር እናቱ) ናት።" የሚል ነው።
እመቤታችንን፦
የአምላክ እናት፣
ዘላለማዊት ድንግል፣ ፍጽምት፣ ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና።

ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን። እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች።" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው። ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ።" ብሎ ረገመው። ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ።

እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሒዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች።

ቅዱስ ቄርሎስ ግን ለሠላሳ ሁለት ዘመናት በመንበሩ ላይ አገልግሎ፣ ፍሬ ትሩፋት አፍርቶ፣ ብዙ ድርሰቶችንም ደርሶ በ፬፻፵፬ ዓ.ም በዚህች ቀን ዐርፏል። ከድርሰቶቹም ቅዳሴው፣ ድርሳነ ቄርሎስና ተረፈ ቄርሎስ ይጠቀሳሉ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችን ጸሎት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን። ከሊቁም በረከቱን ይክፈለን።

ሐምሌ ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)
፪.ቅዱስ ክልስቲያኖስ ዘሮሜ (ታላቅ ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት)
፫.አባ ሉቅያስ ኤጲስ ቆጶስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
፬.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭.አቡነ ዜና ማርቆስ
፮.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

"የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ። የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ። ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም። በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።"
(ዕብ ፲፫፥፯-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…
Subscribe to a channel