gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ አንስጣስዮስ <3

የግብጽ ሠላሳ ስድስተኛ ፓትርያርክ የሆነው ይህ አባት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተወለደ ሲሆን በትጋቱ፣ በትምህርቱና በድርሰቱ ይታወቃል። ምዕመናንን ለማስተማር ከአሥራ ሁለት ሺህ በላይ ድርሰቶችን ደርሷል። ብዙ መከራዎችን አሳልፎ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዐርፏል።

<3 ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል <3

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከሰባቱ ሊቃናት አንዱ፣
በራማ አርባብ በሚባሉ አሥር ነገደ መላእክት ላይ የተሾመ፣
በመጀመሪያዋ የፍጥረት ቀን መላእክትን ያጸና፣
ቅዱሳንን ሁሉ የሚረዳ፣
ሠለስቱ ደቂቅን፣ ዳንኤልንና ሶስናን ከሞት የታደገ ታላቅ መልአክ ነው።

ከምንም በላይ ቤተ ክርስቲያን "መጋቤ ሐዲስ" ብላ ታከብረዋለች። የስሙ ትርጓሜ "አምላክ ወሰብእ - እግዚእ ወገብር" ነውና ለሥነ ፍጥረት ሁሉ የሚሆን ሐዲስ ዜናን ወደ እመቤታችን ድንግል ማርያም አምጥቷል።
መልአኩ እመቤታችንን ከመጸነሷ ጀምሮ ባይለያትም ከእግዚአብሔር ተልኮ አብስሯታል።

ቅዱስ ገብርኤል ዛሬ የብሥራቱ መታሰቢያና ዳናህ በተባለ ሃገር ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ነው።
"ገብርኤል ዜናዊ ምጽዓተ ክርስቶስ አንበሳ
ለዛቲ በዓልከ በዘይትሌዓል ሞገሳ
በዓለ ማርያም አንበረ ደቅስዮስ በርዕሳ።" እንዲል።
(አርኬ)

ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን። አዕምሮውን ጥበቡን በልቡናችን አሳድሪብን።

ታኅሣሥ ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ተአምረ ማርያም
፪.ቅዱስ ደቅስዮስ ጻድቅ
፫.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፬.ቅዱስ አንስጣስዮስ ሊቅ
፭.አባ አርኬላዎስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.አባ እንጦንስ
፫.አባ ጳውሊ የዋህ
፬.ቅዱስ ዮልዮስ
፭.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ

"የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው። መንፈስ ግን አንድ ነው። አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው። ጌታም አንድ ነው።
.....ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር.....ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ.....ይሰጠዋል።"
(፩ቆሮ ፲፪፥፬-፲)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ በርናባስ ሐዋርያ <3

ቅዱሱ ሐዋርያ ስሙ ሲጠራ ሞገስ አለው። የቅዱሱ ሰው የመጀመሪያ ስሙ ዮሴፍ ሲሆን በርናባስ ያለው መድኃኒታችን ክርስቶስ ነው። ትርጉሙም "ወልደ ኑዛዜ - የመጽናናት ልጅ" እንደ ማለት ነው።

በምሥጢሩ ግን "ማሕደረ መንፈስ ቅዱስ - የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ" እንደ ማለት ያስተረጉማል። ቅዱስ በርናባስ ምንም በትውልዱ እስራኤላዊ ቢሆን ተወልዶ ያደገው በቆጵሮስ ነው። እስከ ወጣትነት ጊዜውም የቆየው እዚያው ነው።

የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰው የመሆኑ ዜና ሲሰማ ግን ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ መድኅን ክርስቶስን ተመለከተ። ጌታውንም ሊከተል በልቡ ቆረጠ። የፈጠረን ክርስቶስም እንዲረባ (እንዲጠቅም) አውቆ ስሙን ቀይሮ አስከተለው። ከሰባ ሁለቱ አርድእትም ደመረው።

ቅዱስ በርናባስ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ እግር ቁጭ ብሎ ተማረ። ተአምራቱንም ሁሉ ተመለከተ። ከጌታ ዕርገት በኋላ መቶ ሃያው ቤተሰብ በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩም አብሮ ይተጋ ነበር።

በጊዜውም አበው ሐዋርያት በይሁዳ ፈንታ ከአሥራ ሁለቱ የሚቆጠረውን ሰው ለመምረጥ ሁለት ሰዎችን አቅርበው ነበርና አንዱ ይኸው ቅዱስ ነው። እዚያውም ላይ ጌታችንን ከመጀመሪያው ጀምሮ ማገልገሉ ተመስክሮለታል።
(ሐዋ. ፩፥፳፪)

ስሙንም ኢዮስጦስ ብለውታል። ባለ ሦስት ስም ነበርና። በወቅቱም ዕጣ በቅዱስ ማትያስ ላይ ስለ ወደቀ በርናባስ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ማትያስ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሆነው ቀጠሉ።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ በርናባስ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ በኃይል ያገለግል ጀመር። የሐዋርያትን ዜና በሚናገር መጽሐፍ ላይ የተጻፉና ስለ ቅዱሱ ማንነት የሚናገሩ ክፍሎችን እንመልከት።

፩.ቅዱሳን ሐዋርያት የእኔ የሚሉት ንብረት ሳይኖራቸው ያላቸውን በጋራ እየተጠቀሙ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ነበር። ያለውን ሁሉ ሸጦ በሐዋርያት እግር ላይ በማኖር ደግሞ ቀዳሚውን ሥፍራ ቅዱስ በርናባስ ይይዛል።
(ሐዋ. ፬፥፴፮)
በዚህም የዘመነ ሐዋርያት የመጀመሪያው መናኝ ተብሏል።
፪.ልሳነ እፍረት (ብርሃነ ዓለም) ቅዱስ ጳውሎስ ባመነ ጊዜ ሐዋርያት ለማመን ተቸግረው ነበር። የሆነውን ሁሉ አስረድቶ ቅዱስ ጳውሎስን ከሐዋርያት ጋር የቀላቀለው ይህ ቅዱስ ነው።
(ሐዋ. ፱፥፳፮)
፫.አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ "ፍልጥዎሙ ሊተ ለሳውል ወለበርናባስ - በርናባስና ሳውልን (ጳውሎስን) ለዩልኝ።" በማለቱ ሐዋርያት ጾመው ጸልየው እጃቸው ከጫኑባቸው በኋላ ላኳቸው።
(ሐዋ. ፲፫፥፩)
እነርሱም ወንጌልን እየሰበኩ በየሃገሩ ዞሩ። በሃገረ ልስጥራን መጻጉዕን ስለ ፈወሱ ሕዝቡ "እናምልካችሁ" ብለው የአማልክትን ስም አወጡላቸው። ሁለቱ ቅዱሳን ግን ይህንን ሲሰሙ ልብሳቸውን ቀደው በጭንቅ አስተዋቸው። መመለክ የብቻው የፈጣሪ ገንዘብ ነውና።
(ሐዋ. ፲፬፥፰-፲፰ ፣ ዘጸ. ፳፥፩)
፬.በአንጾኪያ የነበሩ አሕዛብ ክርስትናን በተቀበሉ ጊዜ ከሐዋርያት ተልኮ ሒዶ በጐ ጐዳናን መራቸው።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፪)

ቅዱስ በርናባስ በአገልግሎት ዘመኑ መጀመሪያ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ቀጥሎ ደግሞ ቅዱስ ማርቆስን አስከትሎ ብዙ አሕጉራትን አስተምሯል። ቆጵሮስም ሃገረ ስብከቱ ናት።

ቅዱሱ ከብዙ ትጋት በኋላ በዚህች ቀን አረማውያንና አይሁድ ገድለውታል። ቅዱስ ማርቆስም ገንዞ ቀብሮታል።
ስለርሱ መጽሐፍ "ደግ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ነው።" ይላልና ክብር ይገባዋል!
(ሐዋ. ፲፩፥፳፬)

<3 አባ ይስሐቅ ጻድቅ <3

ይህ ቅዱስ በመካከለኛው ዘመን በምድረ ግብጽ የነበረ ገዳማዊ ነው። መንኖ ለብዙ ዘመናት በገዳም ሲኖር ምኞቱ አንዲት ብቻ ነበረች። እመቤታችንን በአካል መመልከትን ይፈልግ ነበር።

የገዳሙ ጠባቂ በመሆኑ መነኮሳት ሲተኙ መቅደሱን ከፍቶ በድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ይጸልይ፣ ይሰግድ፣ ያነባ ነበር። እንዲህ ለሰባት ዓመታት ስለ ተጋ ድንግል እመ ብርሃን ልመናውን ሰማች።

በዚህ ዕለትም ከፀሐይ ሰባት እጅ ደምቃ ወደ እርሱ መጣች። ደንግጦ ሲወድቅ አነሳችው። "ከሦስት ቀናት በኋላ እመለሳለሁ።" ብላም ተሠወረችው። በሃያ ሦስት ቀንም ዐረፈ።
"በዛቲ ዕለት ሶበ ጸለየ ጥቡዐ
ለይስሐቅ አስተርዓየቶ እም አይቆናሃ ወጺአ
እምጸዳለ መብረቅ ጥቀ እንዘ ትጸድል ስብአ።" እንዳለ ደራሲ።
(አርኬ)

የእስራኤል እረኛ ሥጋችንን ከመቅሰፍት ነፍሳችንን ከገሃነመ እሳት ይጠብቅልን። ከበረከተ ቅዱሳንም ይክፈለን።

ታኅሣሥ ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ኖላዊ ሔር
፪.ቅዱስ በርናባስ ሐዋርያ
፫.አባ ይስሐቅ ጻድቅ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም
፪.አበው ጎርጎርዮሳት
፫.አቡነ ምዕመነ ድንግል
፬.አቡነ አምደ ሥላሴ
፭.አባ አሮን ሶርያዊ
፮.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

"መልካም እረኛ እኔ ነኝ። አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጐች አውቃለሁ። የራሴም በጐች ያውቁኛል። ነፍሴንም ስለ በጐች አኖራለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጐች አሉኝ። እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል። ድምጼን ይሰማሉ። አንድም መንጋ ይሆናሉ።"
(ዮሐ ፲፥፲፬-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ቅዱስ ሐጌም በሕጉ እየኖረ ትንቢትን እየተናገረ ዘመኑን ፈጽሟል። በትውፊት ትምህርትም ቅዱሱ የተወለደው በ፭፻ ዓ/ዓ ሲሆን ያረፈው በሰባ ዓመቱ ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ ሠላሳ ዓመታት በፊት ነው።

አምላከ ሐጌ ለቤቱ የምናስብበትን ዘመን ያምጣልን። ከቅዱሱ ነቢይ በረከትም ይክፈለን።

ታኅሣሥ ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሐጌ ነቢይ
፪.አባ አውጋንዮስ
፫.ታውፊና ንግሥት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፪.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፫.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፬.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፭.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
፮.ማር ቴዎድሮስ ኃያል ሰማዕት

" 'ብሩ የእኔ ነው። ወርቁም የእኔ ነው።' ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 'ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል።' ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። በዚህም ሥፍራ ሰላምን እሰጣለሁ።"
(ሐጌ ፪፥፰-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ገብርኤል ሆይ! ከጭንቅና ከመከራ ለማውጣት የተላክህ መልአክ ነህና ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ጉድጓድ በተጣሉ ጊዜ ሁለቱ ክንፎችህን ጋርደህ ከመቃጠል እንዳዳንሃቸው እኔንም አገልጋይህን በረድኤትህ ኃይል አድነኝ።"
(መልክአ ገብርኤል)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ዮሐንስ ዘቡርልስ እና አቡነ ስነ ኢየሱስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት <3

በቤተ ክርስቲያን ክቡር ከሆኑ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ገብርኤል ብዙ የክብር ስሞች አሉት።
በተለይ ግን፦
ሊቀ አርባብ፣
መጋቤ ሐዲስ፣
መልአከ ሰላም፣
ብሥራታዊ፣
ዖፍ አርያማዊ፣
ፍሡሐ ገጽ፣
ቤዛዊ መልአክ፣
ዘአልቦ ሙስና.....እየተባለ ይጠራል።

በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ስሙ በብዛት ተጠቅሷል። ስለ ረዳትነቱና አማላጅነቱም ቤተ ክርስቲያን በስሙ ታቦት ቀርጻ መቅደስ አንጻ በሥርዓት ክብሩን ትገልጻለች።

ከእነዚህም አንዱ ሠለስቱ ደቂቅን እንዳዳነ የሚታሰብበት በዓሉ ዛሬ ነው።
"ለዝንቱ ዜናዊ መልአከ ኃይል
በዛቲ ዕለት ከመ ይትገበር በዓል
መምሕራን አዘዙ ወሠርዑ በቃል።" እንዲል።
(አርኬ)

ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግሥት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር። ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ።

ምንም እንኳ በቤተ መንግሥት ውስጥ ቢኖሩ ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ።

አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከእነርሱ የሚደርስ አልተገኘም። ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው። ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው።

ከነገር ሁሉ በኋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ። ናቡከደነጾር ስልሳ ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ ስገዱ ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው። ነበልባሉ ከጉድጓዱ ወደ ላይ አርባ ዘጠኝ ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም።

ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልአከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው። ከሆነው ነገር የተነሳ አሕዛብ አፈሩ። ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ።

ቅዱሳኑን ያዳነ ቅዱስ መልአክ እኛንም ያድነን ዘንድ እንደ አባቶቻችን
"አድኅነኒ ዘአድኃንኮሙ በአክናፊከ ምንትው
አመ ውስተ እሳት ተወድዩ ሠለስቱ እደው።" እያልን እንለምነው።
(መልክአ ገብርኤል)

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ዘቡርልስ <3

ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ የከበረ ነው። ሊቅም፣ ጻድቅም፣ ጳጳስም፣ ገዳማዊም ነው። ከሁሉም በላይ ግን ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን በተድላ ለምትጠቀምባቸው መጻሕፍት (ስንክሳር፣ ግጻዌ እና ሃይማኖተ አበው) መሠረትን የጣለ ቅዱስ ሰው ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ በትውልዱ ግብጻዊ ሲሆን ጊዜውም አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ወላጆቹ ክርስቲያኖች በዚያውም ላይ ሞልቶ የተረፋቸው ባለ ጠጐች ነበሩ። እንደ ሕጉ ወጣት እስኪሆንና ራሱን እስኪችል ድረስ አሳደጉት።

ከዚያ ግን ድንገት አባቱና እናቱ ተከታትለው ዐረፉ። ከቁጥር የበዛ ሃብትን የግሉ ያደረገው ቅዱስ ዮሐንስ ምን እንደሚያደርግበት ጨነቀው። አንድ ትልቅ ነገር ግን ከማይሆን ጐዳና ጠበቀው።

ወላጆቹ ሁሌም መዝገብን በሰማያት ያገኙ ዘንድ ለነዳያን ይራሩ ነበርና ይህንኑ ለመቀጠል ወሰነ። መልካም ፍሬ ከመልካም ዛፍ ነውና (ማቴ. ፯፥፲፮) ወላጅ ለልጁ ማውረስ ያለበት ምድራዊ ሃብትን ሳይሆን በጐ ሕሊናን ነው። ሳይሠሩ ያገኙት ሃብት ብዙዎችን አጥፍቷቸዋል።

ለዚያም ይመስላል ዛሬ አንዳንዶቻችን በቤተሰቦቻችን ሃብት ከእኛ አልፈን ትውልዱን እየገደልንበት ያለው። ለዚህ ደግሞ እግዚአብሔር ንስሐ ካልገባን ይመጣብናል። መቅረዛችን (ሕይወታችንም) ከእኛ ላይ ይወስዳል።

ፍርድ የሚሆነው በክፉው ትውልድ ላይ ብቻ አይደለም። ይህንን ትውልድ በፈጠርነውና መልካሙን መንገድ ባልመራነው በሁላችንም ላይ እንጂ።
(ራእ. ፪፥፭)

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ ዮሐንስ በወላጆቹ ሃብት የእንግዶች ማረፊያ የሚሆኑ ቤቶችን አንጾ ነዳያንን ይንከባከብ ገባ። ሙሉውን ቀን ለነዳያን ሲራራ ይውላል። አመሻሽ ላይ እንግዶችን ተቀብሎ አብልቶ ያሳርፋል።

ከዚያም ፈጣሪውን ያመሰግናል። በእንዲህ ያለ ሕይወት ዘመናትን ካሳለፈ በኋላ አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤቱ መጣ። አስተናግዶት ሲጨዋወቱ አደሩ። ሌሊት ላይ ግን ስለ ምንኩስና ሕይወትና ስለ ክብሩ ነግሮት ነበርና ልቡ ተመሰጠ።

መነኮሱን ከሸኘው በኋላም ይመንን ዘንድ ቆረጠ። ነዳያንን ሰብስቦ ሃብቱን አካፈላቸው። ከዚያም ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሒዶ የታላቁ አባ ዳንኤል ደቀ መዝሙር ሆነ። በትሕትና ለአባቶች እየታዘዘ ከቆየ በኋላ በጭንቅ ደዌ ተያዘ። ሰይጣን በቅንዓት ገርፎት ነበርና።

እርሱ ግን በደዌው ምክንያት ለዓመታት መሬት ላይ ወድቆ ቢቆይም ፈጣሪውን ፈጽሞ ያመሰግን ነበር። እግዚአብሔር ደግሞ በፈውስና በኃይል አስነሳው።

በጊዜው የቡርልስ ጳጳስ ዐርፎ ነበርና አባት ፍለጋ ወደ አስቄጥስ ገዳም መጥተው ነበር። መንፈስ ቅዱስ መርጦታልና አበው ቅዱስ ዮሐንስ ጳጳስ ይሆን ዘንድ አስገደዱት። እርሱም የፈጣሪ ፈቃድ መሆኑን ስላወቀ ሔደ።

በዚያም (በሃገረ ቡርልስ) ታላቁን ገድል ተጋደለ። ወደ ከተማዋ ሲገባ ብዙ ነገሮች ከሚገባው ሥርዓት የወጡ ነበሩ። ብዙ ሰው የእግዚአብሔርን ድምጽ ከመስማት ይልቅ ባላስፈላጊ ነገሮች ላይ ተጠምዶ ነበርና መንጋውን ያድን ዘንድ ተጋ።

ሳይሆኑ "ባሕታዊ"፣ "አጥማቂ" ነን እያሉ ሕዝቡን የሚያሳስቱ ተኩላዎችንም አስወገደ። ለሕዝቡ አጉል ሕልም ሟርትን የሚያስተምሩትን ገሠጸ። አንመለስም ያሉ መናፍቃንን እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው።

ቅዱስ ዮሐንስ ከቅድስናው ብዛት ዘወትር ሲቀድስ መድኃኒታችንንና አእላፍ መላእክትን ያይ ነበር። ከከዊነ እሳት ማዕረግ በመድረሱም አካሉ በመፈተት ሰዓት እንደ እሳት ይነድ ነበር። እንባውም እንደ ውኃ ይፈስ ነበር።

ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ ጐን ዛሬም ድረስ የሚታወቅበትን ታላቅ ሥራም ሠርቷል። መንፈስ ቅዱስ አነሳስቷቸው ቅዱሱና የሃገረ አትሪብ ጳጳስ የነበረው ሊቁ አባ ሚካኤል መጽሐፈ ስንክሳርን፣ መጽሐፈ ግጻዌንና ሃይማኖተ አበውን ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅተዋል።

"ስንክሳር" የቅዱሳንና የፈጣሪን ነገር በየዕለቱ የሚዘግብ መጽሐፍ ሲሆን "ግጻዌ" የየዕለቱን በዓላት ከምስባክና ምንባባት ጋር አስማምቶ የያዘ መጽሐፍ ነው። "ሃይማኖተ አበው" ደግሞ የዶግማ መጽሐፍ ሆኖ ከሐዋርያት እስከ ሊቃውንት ድረስ የጻፉትን የያዘ ነው። ሦስቱን የሚያመሳስላቸው "ስብስብ /እስትጉቡዕ/ Collection" መሆናቸው ነው።

ቅዱሱ ዮሐንስ በሃገረ ቡርልስ በከፍተኛ ድካም ይህንን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል።

<3 አቡነ ስነ ኢየሱስ ጻድቅ <3

ጻድቁ በመካከለኛው (የብርሃን) ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያዊ፣
ከምድረ ሽዋ ወደ ታች አርማጭሆ የሔዱ መናኝ፣
ጭው ባለ በርሃ ለቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ ገዳምን ያነጹ አባት፣
ብዙ አርድእትን ያፈሩ መናኝ፣
ብዙ ተአምራትን የሠሩና ወንጌልን ያስተማሩ መነኮስ ናቸው።

በደመናም ይጫኑ ነበር። ገዳማቸውም (ታች አርማጭሆ ከሳንጃ ከተማ የሦስት ሰዓት መንገድ ይወስዳል።) ድንቅና ባለ ብዙ ቃል ኪዳን ነው። መልአከ ሞት መስከረም ፩ ቀን ቢመጣ "የቅዱስ ገብርኤልን በዓል ሳላከብር አይሆንም።" ብለው ለሦስት ወራት በበራቸው አቁመውታል። ታኅሣሥ ፲፱ ቀንም ዐርፈዋል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሐዋርያት ቶማስ ወቲቶ እና ለአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ <3

ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ብዙ መከራን በማሳለፉና የጌታችንን ጐን በመዳሰሱ ይታወቃል።

ቅዱስ ቶማስ እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት በእስራኤል ተወልዶ በዚያውም በሥርዓተ ኦሪት አድጐ ገና በወጣትነቱ የሰዱቃውያንን ማኅበር ተቀላቅሏል። ሰዱቃውያን ሰው ከሞተ በኋላ አይነሳም (አልቦ ትንሣኤ ሙታን) የሚሉ ናቸው። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተማር ሲጀምር ግን ቅዱስ ቶማስ ከነበረበት ማኅበር ወጥቶ ጌታችንን ተከተለ። ጌታችንም ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ይሆን ዘንድ ሾመው። የቀደመ ስሙ "ዲዲሞስ" ሲሆን ጌታችን "ቶማስ" ብሎታል።

ቅዱስ ቶማስ ጌታ አልዓዛርን ለማስነሳት በሔደ ጊዜ ሌሎች ሐዋርያት ጌታን "አይሁድ ይገድሉሃል ቅር።" ሲሉት እርሱ ግን "እንሒድና አብረን እንሙት።" ሲል ፍቅሩን አሳይቷል።
(ዮሐ. ፲፩፥፲፮)

ጌታችን ትንሣኤውን ለደቀ መዛሙርቱ በገለጠ ጊዜ ያልነበረው ቶማስ ካላየሁ አላምንም አለ። ምክንያቱም፦
፩.ለጌታችን ከነበረው ፍቅር የተነሳ እውነት አልመስልህ ቢለው።
፪.አንድም "ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን አየን እያሉ ሲያስተምሩ እኔ ግን ሰማሁ ብየ ማስተማሬ ነው።" ብሎ በማሰቡ ነበር።

ለጊዜው ጌታ ተገልጾ ቢገስጸው "እግዚእየ ወአምላኪየ (ጌታዬና አምላኬ)" ብሎ ፍጹም ሃይማኖቱን ገልጿል። ለፍጻሜው ግን የጌታችንን ጎን (መለኮትን) ይዳስስ ዘንድ ባለቤቱ እንዳደለው ያጠይቃል። መለኮትን የዳሰሰች ይህቺ ቅድስት እጁ ዛሬም ድረስ ሕያው ናት።

ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ሃገረ ስብከት ሲከፋፈሉ ለቅዱስ ቶማስ ሕንድና በዙሪያዋ ያሉ ሃገራት ደረሱት።

ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ዘርዝረን የማንጨርሰውን ተጋድሎ የፈጸመው። ቅዱሱ በነበረው ፍጹም ትጋት አባቶቻችን "ዘአሠርገዋ ለብሔረ ሕንደኬ (ሕንድን በወንጌል ያስጌጣት)" ሲሉ ያከብሩታል።

ቅዱስ ቶማስ ንጉሥ ሉክዮስንና የሃገሩን ሕዝብ ለማሳመን በችንካር መሬት ላይ ወጥረው ቆዳውን ገፈውታል። ቆዳውንም እንደ ገና ሰፍተው አሸዋ ሞልተው አሸክመውታል። በየመንገዱ የተገፈፈ ገላውን ጨው ቢቀቡት በጎች መጥተው ግጠው በልተውታል።
በዚህ ምክንያት፦
"ኩሉ የአኪ እንዘ የአኪ ዘመኑ
አባግዒሁ ለቶማስ እስመ አራዊተ ኮኑ።" ብለዋል ሊቃውንቱ።

በኋላ ግን ከፎቅ ወድቃ የሞተችውን የንጉሡን ሚስት በተገፈፈ ቆዳው በማዳኑ ሁሉም አምነው ተጠምቀዋል።

ቅዱሱ ሐዋርያ ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አንዳንዴ በፈሊጥ ሌላ ጊዜም በመከራ ለወንጌልና ለቤተ ክርስቲያን ተጋድሏል። ያለ ማቋረጥም ከሕንድ እስከ ሃገራችን ኢትዮጵያ ድረስ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ወንጌልን ሰብኳል። በመጨረሻም በ፸፪ ዓ/ም በሰማዕትነት ዐርፏል። መቃብሩና ቅድስት እጁ ዛሬ ድረስ ሕንድ ውስጥ አሉ። ከኘሮቴስታንቶች በቀር መላው ዓለም ያከብረዋል። ዛሬ የቅዱሱ ሐዋርያ በዓለ ፍልሠቱ ነው።

<3 ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያ <3

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ቲቶ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሲሆን በተወሰነ መንገድም ቢሆን የተዘነጋ ሐዋርያ አይደለም። በተለይ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፋቸው አሥራ አራት መልእክታት መካከል አንዷ የተላከችው ለዚህ ቅዱስ በመሆኗ ታሪኩ ባይነገር እንኳ ስሙ አይረሳም። ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክታቱ በጐ ስሙን እየደጋገመ ያነሳዋል።

ቅዱስ ቲቶ የተወለደው በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስያ ውስጥ ቀርጤስ በምትባል ከተማ ነው። መዳን በእውቀት ይመስላቸው ስለ ነበር የአካባቢው ሰዎች የግሪክን ፍልስፍና ጠንክረው ይማሩ ነበር። ቅዱስ ቲቶም በወጣትነቱ ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ የግሪክን ፍልሥፍናና የዮናናውያንን ጥበበ ሥጋ ተማረ። በጥቂት ጊዜም የሁሉ የበላይ ሆነ።

ቅዱሱ ምክንያቱን ሳያውቀው ለእኔ ቢጤዎች ያበላ፣ ያጠጣ፣ ይንከባከባቸውም ነበር። እግዚአብሔር ግን የዚህ ቅን ሰው በጐነቱ እንዲሁ እንዲቀር አልወደደምና አንድ ቀን በራእይ ተገለጠለት።

በራእይም አንድ ምንነቱን ያልተረዳው ነገር "ቲቶ ሆይ! ስለ ነፍስህ ድኅነት ተጋደል። ይህ ዓለም ኃላፊ ነው።" ሲለው ሰማ። ከእንቅልፉ ነቅቶ በእጅጉ ደነገጠ። የሚያደርገውንም አጣ። ያናገራቸው ሁሉ ምንም ሊገባቸው አልቻለም።

ድንገት ግን በዚያ ሰሞን ከወደ ኢየሩሳሌም አዲስ ዜና ተሰማ። "ክርስቶስ የሚሉት ኢየሱስ እርሱም የባሕርይ አምላክ የሆነ ወደ ምድር ወርዶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየሰበከ ነው።" ሲሉ ለቲቶ ነገሩት።

"ሌላስ ምን አያችሁ?" አላቸው። "በእጆቹ ድውያን ይፈወሳሉ፣ ሙታን ይነሳሉ፣ እውራን ያያሉ፣ ለምጻሞች ይነጻሉ፣ ሌሎች ብዙ ተአምራትም እየተደረጉ ነው።" አሉት። የወቅቱ የሃገረ አክራጥስ መኮንን ፈላስፋ ነበርና ስለ ክርስቶስ ሲሰማ ሊመራመር ወደደ።

"ብልህ ጥበበኛ ሰው ፈልጉልኝ።" ብሎ ተከታዮችን ቢልካቸው ከቲቶ የተሻለ በአካባቢው አልነበረምና እርሱኑ አመጡት። መኮንኑ ቲቶን "ነገሩ ትክክል ወይም ስሕተት መሆኑን በጥልቅ መርምረህ ምላሽ አምጣልኝ።" ብሎ ላከው።

ቅዱስ ቲቶም ፈጥኖ ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ገሰገሰ። ወደ ከተማዋ እንደገባም ጌታችንን አፈላልጐ አገኘው።

፩.ጌታችን ክርስቶስ በሥልጣነ ቃሉ ደዌያትን ሲያርቅ አጋንንትን ሲያሳድዳቸው ተመልክቶ ይህ ሥራ የፍጡር እንዳልሆነ ተረዳ።
፪.ጌታችን የሚያስተምረው ትምህርት ከግሪክ ፍልሥፍና እጅግ ርቆና መጥቆ አገኘው። ጌታ በጣዕመ ቃሉ የሚያስተምረው ሰማያዊ በዚያ ላይ ዘላለማዊ የሆነ ትምህርት ነው። በራእይ "ስለ ነፍስህ ተጋደል።" ያለው ምሥጢር አሁን ተተረጐመለት።

በዚህ ምክንያትም ጊዜ አላጠፋም። ወዲያውኑ አምኖ ተከታዩ ሆነ። ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደመረው። የአክራጥስ መኮንን "ምነው ዘገየህ?" ቢለው ያየውን ሁሉ ጽፎ እንደማይመለስም አክሎ ደብዳቤ ላከለት።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ከጌታችን እግር ለሦስት ዓመታት ተምሮ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ በመላው እስያ ወንጌልን ሰብኳል። ቅዱስ ጳውሎስ ባመነ ጊዜ ደግሞ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆኖ ለሃያ አምስት ዓመታት አስተምሯል።

ቅዱስ ጳውሎስ ሰማዕት ከሆነ በኋላ ደግሞ ወደ አክራጥስ ተመልሶ ሕዝቡን አሳምኖና አጥምቆ ቤተ ክርስቲያንን አንጿል። ዕድሜው በደረሰ ጊዜም መምህራንን፣ ካህናትን ሹሞላቸው ባርኳቸውም ዐርፏል።
ዛሬ የቅዱሱ ሐዋርያ በዓለ ፍልሠቱ ነው።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ጻድቅ ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ <3

"ዘዓምድ" በሚል ስም ከሚታወቁ የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል አራቱ ቅድሚያውን ይይዛሉ።
እነዚህም፦
ቅዱስ ስምዖን ዘዓምድ፣
ቅዱስ አጋቶን ዘዓምድ፣
ቅዱስ ዳንኤል ዘዓምድ እና
ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ ናቸው።

"ዘዓምድ" የሚለውን ቃል ምሥራቃውያን በልሳናቸው "THE STYLITE" ይሉታል። የእኛው ቃል ደግሞ ከግዕዝ የተወረሰ ነውና በቁሙ ቢተረጐም "የምሰሶው" የሚል ትርጉምን ይይዛል። ይህም በሁለት ምክንያቶች ነው።

አንደኛው ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን የፈጸሙት ከረዥም ምሰሶ ላይ ወጥተው በመጸለይ ስለሆነ ነው። ሌላኛው ምክንያት ደግሞ እነዚህ አባቶች በዘመኑ ለነበሩ ምዕመናንና መነኮሳት አጽናኝ፣ አስተማሪ፣ መሪና ፈዋሽ በመሆናቸውና እንደ ምሰሶ ተተክለው ሳይነቃነቁ በመጸለያቸው ነው።

ልክ ከዓለም ሃገራት ብዙ ስውራንን እና ቅዱሳን ነገሥታትን በመያዝ ሃገራችን ቀዳሚ እንደ ሆነችው ሁሉ ምሰሶ ላይ ወጥተው የሚጋደሉ ቅዱሳንም ሶርያውያንና ምሥራቃውያን ናቸው። በዚህ ዕለትም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የታላቁን ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድን በዓል ታከብራለችና ከዜና ሕይወቱ ለበረከት ጥቂት እንካፈል።

ቅዱስ ሉቃስ ተወልዶ ያደገው በፋርስ (በአሁኗ ኢራን) ሲሆን ዘመኑም ዘመነ ጻድቃን (ከሦስተኛው እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ) እንደ ሆነ ይታመናል። ዛሬን አያድርገውና በጊዜው በጣም ብዙ በዚያም ላይ ጽኑዕ የሆኑ ክርስቲያኖች በሃገሪቱ ነበሩ።

በወቅቱ በየሥፍራው ዜና ቅዱሳን ሰፍቶ ነበርና ብዙዎቹ ወደ ምናኔ እየሔዱ ገዳማትን አጨናንቀው ነበር። መንፈሳዊ ቅንዓት የሚያቃጥላቸው ክርስቲያኖችም ብዙ ነበሩ።

ቅዱስ ሉቃስ ከልጅነቱ መሠረቱ ክርስትና ነው። ልጅ ሳለም ሃይማኖቱን በሚገባ አውቋል። ወጣት በሆነ ጊዜ ሠርቶ መብላት ሃይማኖታዊ ግዴታም ነውና ሥራ ፍለጋ ወጣ።

በጊዜው ደግሞ በቀላሉ የሚገኝ ሥራ የሠራዊት አባል ወይም በዘመኑ ልሳን "ወታደር" መሆን ነበርና ሒዶ ገባ። ውትድርና የኃጢአት ሥራ አይደለም። ሃገርን፣ ዳርን፣ ድንበርን እየጠበቁ ራስን መስዋእት ማድረግ ነውና።

ነገር ግን አንዳንዶቻችን የማይገባ ሥራ ስንሠራበት ለእኛም ለወገንም የማይበጅ ድርጊት ስንፈጽም ይታያል። ለዚህ ደግሞ እግዚአብሔር በምድርም ሆነ በሰማይ ይፈርዳልና ሁላችንም በተሠማራንበት ሙያ ሁሉ እንደሚገባ ልንኖር ግድ ይለናል። የአባቶች ሕይወት እንዲህ ነበርና።

ቅዱስ ሉቃስም ወታደር (ጭፍራ) ነው። ግን ደግሞ ክርስቲያን ነው። በሁለቱም ማንነቶቹ የሚጠበቁበትን እየተወጣ የወጣትነት ስሜቱን በፈጣሪው ኃይል እየገታ ራሱን ለእግዚአብሔር እያስገዛ ቀጠለ።

እንደሚታወቀው ሰው በሥራው መጠን ክፍያው (ደሞዙ) እና ማዕረጉ (ሥልጣኑ) ከፍ እያለ መሔዱ አይቀርም። ምንም እንኳ ብዙ እንዲህ ዓይነት ተግባራት በዘመናችን ቀዝቃዞች ቢሆኑም። የሠራውን ትቶ ላልሠራው መሸለም በክርስትናው ዓለም ትልቅ ስህተት ነው።

ምናልባትም ይሔው ገርሞት ይመስለኛል፦
"ሃገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ።" ሲል የሃገራችን ሕዝብ የተቀኘው።

ቅዱስ ሉቃስም እንደ ሥራው መጠን ከፍ እያለ ሒዶ የፋርስ ሠራዊት ሃቤ ምዕት (የመቶ አለቃ) ለመሆን በቃ።

ቅዱስ ሉቃስ የጦር መሪነት ሥራውን እያከናወነ ጐን ለጐን ለፈጣሪው ይገዛ መጻሕፍትን ያነብ ነበር። በተለይ ዜና ቅዱሳን ዕለት ዕለት ይስበው ነበርና ልቡናው ወደ ፍቅረ ክርስቶስ ተመሰጠ። ይህችን ዓለም ትቷት ሊሔድም ተመኘ።

በጐ ምኞትን የሚፈጽም ጌታም ልቡን አበርትቶለት ከዓለማዊ ንብረቱ አንድም ነገርን ሳያስከትል ሹመቱንም ትቶ በርሃ ገባ። በዚያም በረድዕ ሥርዓት የአባቶች ደቀ መዝሙር ሆነ። አዛዥነትን ትቶ ታዛዥ ተገልጋይነትን ትቶ አገልጋይ ሆነ።

ትሕትናውንና ትጋቱን የተመለከቱ አበውም ወደ ምንኩስና ማዕረግ ከፍ አደረጉት። አሁንም ታጥቆ አገልግሎቱን ቀጠለ። እውቀቱን፣ ማስተዋሉንና ቅድስናውን ያዩ አባቶች በጐ እረኛ እንደሚሆን ስላወቁም ቅስናን ሾሙት።

ከዚህ በኋላ ግን ቅዱስ ሉቃስ የተጋድሎውን ደረጃ ከፍ አደረገ። በመጀመሪያ ጾሙን ከአንድ ቀን ወደ ሦስት ቀን አሸጋገረ። ትንሽ ቆይቶ ግን ጾሙ ሰባት ቀን ሆነ። ምን ጊዜም እህልን የሚቀምሰው በዕለተ ሰንበት (እሑድ) ብቻ ሆነ።

ሁልጊዜም በዕለተ ሰንበት ቅዳሴን ይቀድሳል። ለእርሱ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ለሌሎቹ ያቀብላል። ከዚያም ወደ በዓቱ ሒዶ አንዲት ጳኩሲማን ይመገባል። "ጳኩሲማን" አባቶች በቀደመ ልሳን "የዳቦ ለከት" ይሉታል። በዘመኑ ልሳን "ትንሽ የዳቦ ቁራጭ" እንደ ማለት ነው።

ከዚህ ጐንም ወገቡን በሰንሰለት ታጥቆ በፍጹም መንፈሱ ይጸልይና ይሰግድ ነበር። በዚህ ተጋድሎ ላይ ሳለም በታላቁ አባ አጋቶን ሕይወት መቅናትን ቀና። በአንደበት ከሚወጣ ኃጢአት ይጠበቅ ዘንድም ሙልሙል ድንጋይ አዘጋጅቶ ጐረሰው።

ያ ድንጋይ የሚወጣው በሳምንት አንዴ ለሥጋ ወደሙና ለቁርባን ብቻ ነበር። ማንም ምንም ቢያደርገውም ሆነ ቢናገረው ምንም አይመልስም። ይህም ተጋድሎ "አርምሞና ትዕግስት" ይባላል።

አርምሞ (ዝምታ) አንደበትን መቀደስ ሲሆን ትዕግስት ደግሞ ልብን ጸጥ አድርጐ መቀደስ ነው። ሁለቱ ጸጥ ካሉ ሰውነትም ከኃጢአት ማዕበል ጸጥ ይላልና። የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ማርያምን "ኃርየት መክፈልተ ሠናየ - በጐ እድልን መረጠች።" ያላት ስለዚህ ሃብቷ እንደ ሆነ መተርጉማን አትተዋል።
(ሉቃ. ፲ ፣ ቅዳሴ ማርያም)

ቅዱስ ሉቃስ በዚህ ሕይወቱ ለሦስት ዓመታት ቆየ። በኋላ አምላክ ቅዱስ መልአኩን ልኮ ወደ ቁስጥንጥንያ መራው። የብርሃን መስቀል እየመራውም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ።

በዚያም እስከ ዛሬ ድረስ የሚታወቅበትን ተጋድሎ ጀመረ። ከቁስጥንጥንያ ከተማ አቅራቢያ አንድ ምሰሶ አግኝቶ በላዩ ላይ ወጣ። በዚያም ከእርሱ በፊት የነበሩ ቅዱሳን አባ ስምዖንና አባ አጋቶን ዘዓምድ እንዳደረጉት ያደርግ ጀመር።

በምሰሶው ላይ መቀመጥ ስለ ማይቻል ትልቁና የመጀመሪያው ገድል ያለ ዕረፍት መቆም ነው። በተረፈ ግን ለአካባቢው ምዕመናን መሪ አስተማሪ ነበር። ዝናውን እየሰሙ ሰዎች ከተለያየ አሕጉር ይመጡ ነበር።

ያላመኑትን በስብከቱ ማሳመን ያመኑትንም በምክሩ ማጽናትን ቀጠለ። እርሱ አስተምሮት የማይለወጥ አልነበረም። ምክንያቱም ምሉዓ መንፈስ ቅዱስ (መንፈስ ቅዱስ የመላበት) ነውና አጋንንት በሥፍራው አይቆሙምና።

በጊዜውም ጳጳሳቱም፣ ካህናቱም፣ ሕዝቡም፣ መሳፍንቱም ይወዱት ነበር። ቢያዝኑ አጽናኝ፣ ቢታመሙ ፈዋሽ፣ ከፈጣሪ ቢጣሉ አስታራቂ ነበርና። እንዲህ ባለ ተጋድሎ ቅዱስ ሉቃስ ለአርባ አምስት ዓመታት በምሰሶው ላይ ቆየ። ስለዚህ እስከ ዛሬም ድረስ "ዘዓምድ" (THE STYLITE) እየተባለ ይጠራል።

እግዚአብሔር ሊያሳርፈው በፈለገ ጊዜም ደቀ መዝሙሩን ጠርቶ ወደ ከተማ ላከው። መልእክቱን የሰሙት የቁስጥንጥንያ ከተማ መሳፍንት፣ ጳጳሳት፣ ሕዝቡና ካህናቱ እየተሯሯጡ ቢመጡ ታኅሣሥ ፲፭ ቀን በፍቅር ዐርፎ አገኙት።

እያዘኑ በታላቅ ለቅሶና ዝማሬ ወደ ቁስጥንጥንያ አደረሱት። በዚያም በክብር በዚህች ቀን ከአበው መቃብር ቀበሩት።
ዛሬም ድረስ በአካባቢው ክቡር አባት ነው!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለኃያል መስፍነ እስራኤል ቅዱስ ጌዴዎን እና ማርያም እኅተ ሙሴ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

"ኪዳነ ምሕረት ማርያም አተበቁዓኪ አንሰ
ትቤዝዊ በኪዳንኪ ዘዚአየ ነፍሰ
እስመ በሥራይኪ ለቁስልየ ቅብዕኒ ፈውሰ።"

" ኪዳነ ምሕረት ማርያም ሆይ! በመድኃኒትሽ ቁስሌን እንድትፈውሺ በኪዳንሽ ቤዛነት ነፍሴን እንድታድኚ እማለድሻለሁ።"
(መልክአ ኪዳነ ምሕረት)

<3 ኃያል ጌዴዎን <3

እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው። አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ነቢይና ካህን አድርጐ ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው።

አባታችን አዳም ግን ስሕተት አግኝቶት ከገነት ወጣ። መከራና ፍዳም አገኘው። በኋላም ለመቶ ዓመት አልቅሶ ንስሐ ገባ። ጌታም ንስሐውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ተስፋ ድኅነትን ሰጠው።

ስለዚህም ምክንያት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ትንቢት ሲነገር ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር ምሳሌም ሲመሰል ኖረ። ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ።

ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ። በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም። ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ።

ከእርሱም ይስሐቅ ከዚያም ያዕቆብ (ደጋጉ) ተገኙ። ያዕቆብም "እስራኤል" ተብሎ በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ። በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ረሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው።

በዚያም ለሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ። እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እስራኤልን አሰባቸው። የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው።

ይኸውም በጸናች እጅ በበረታችም ክንድ በዘጠኝ መቅሰፍት በአሥረኛ ሞተ በኩር በአሥራ አንደኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው። በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው። ከዚህ ዘመን ጀምሮም እስራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ።

አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና አሮን በክህነት መሯቸው። ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ በአሮን አልዓዛር ተተኩ። እንዲህ እንዲህ እያለም ከኃያል ሰው ጌዴዎን ደረሱ። ይኸውም ከዓለም ፍጥረት አራት ሺህ አንድ መቶ ሃምሳ አንድ ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው።

በጊዜው እስራኤል ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሔርን ስላሳዘኑት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። የአካባቢው መንግሥታት እነ አሞን፣ አማሌቅ፣ ኢሎፍሊ ስንኳ ያኔ ዛሬም ቢሆን እንደምትመለከቱት ዶሮና ጥሬ ናቸው።

ከክርስቶስ ልደት አንድ ሺህ ሦስት መቶ አርባ ዘጠኝ ዓመታት በፊትም በእስራኤል ላይ ምድያማውያን (ይህቺ ሃገር የኢትዮጵያ ግዛት ነበረች ይባላል።) በጠላትነት ተነስተውባቸው ተጨነቁ።

አምላካችን እግዚአብሔርም ሊያድናቸው ወዶ መልአኩን ወደ ጌዴዎን ላከው። ቅዱስ መልአክም ወደ እርሱ ቀርቦ "ኃያል የእግዚአብሔር ሰው" ሲል ጠራው። ጌዴዎን ግን "ባሮች ስንሆን ምን ኃይል አለን!" ሲል መለሰለት።

መልአኩም "እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነውና ሒድ! እስራኤልን ከምድያም እጅ አድናቸው።" አለው። ጌዴዎን ምልልሱን ቀጠለ። "እግዚአብሔር ከእኔ ጋር መሆኑን በምን አውቃለሁ?" ሲል ጠየቀው።

ጌዴዎን ይህንን ያለው ፈጣሪውን ተጠራጥሮት አይደለም። ይልቁኑ ጥበበ እግዚአብሔር ይገለጥ ዘንድና በኋለኛው ዘመን የሚፈጸመውን ምሥጢረ ሥጋዌ ሊያስረዳ እንጂ።

መልአኩም መስፍኑ የሰዋውን መስዋዕት አሳረገለት። ቀጥሎም ጌዴዎን "ጸምር (ብዝት ጨርቅ) ልዘርጋ። ጠል (ዝናብ) በጸምሩ ላይ ይውረድ። ዳር ዳሩ ግን ይቡስ (ደረቅ) ይሁን።" አለ። በጠዋትም እንዳለው ሆኖ አገኘው።

በጸምሩ ላይ የወረደውን ጠል ጨምቆ በመንቀል ሞልቶ ቢጠጣው ሰማያዊ ኃይል ወረደለት። ጥያቄውን አሁንም ቀጠለ። "ጌታ ሆይ! እንደ ገናም ነገሩ ይቀየርልኝ። ጠል በጸምሩ ላይ አይውረድ። ዳር ዳሩ ግን ይውረድበት።" አለ።

እንዳለውም ሆነ። ይህ ሁሉ ምሳሌ ነው። ለጊዜው ጸምር የእስራኤል፣ ጠል የረድኤት፣ ምድር የአህዛብ ምሳሌ ነው። ጠል በጸምር እንጂ በምድር ላይ እንዳልወረደ ረድኤተ እግዚአብሔር ለእስራኤል እንጂ ለአሕዛብ ያለ መደረጉ ምሳሌ ነው።

አንድም ምሳሌውን ይለውጧል። ጠል የሚለውን ብቻ እንቀይረውና ጠል የመቅሰፍት ምሳሌ በሁለተኛው ጠል በምድር ላይ እንጂ በጸምር ላይ እንዳልወረደ መቅሰፍቱም እስራኤልን ትቶ በአሕዛብ ላይ ወርዷልና። ( ይህ ጊዜያዊ ምሥጢሩ ነው።)

አማናዊ ምሥጢሩ ግን ወደ ሐዲስ ኪዳን ያመጣናል። ጸምር የእመቤታችን፣ ጠል የጌታ ምሳሌ። ጠል በጸምር እንጂ በምድር ላይ አለመውረዱ ጌታ ከድንግል ማርያም ብቻ መወለዱን ያሳያል።

በሁለተኛው ምሳሌ ደግሞ ጠል የፍዳ፣ የመርገም ምሳሌ ይሆናል። ጠል በምድር ላይ እንጂ በጸምር ላይ አለመውረዱ ድንግል ማርያም ፍዳ መርገም የሌለባት ንጽሕት መሆኗን ያሳያል።

ይህ ሁሉ የተደረገለት ጌዴዎንም በወገኖቹ መካከል አዋጅ አስነግሮ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሠራዊትን ሰበሰበ። ግን እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን ክፋት (ማለትም በራሳችን ኃይል አሸነፍን።) እንደሚሉ ያውቃልና "የፈራ ይመለስ በል።" አለው።

ሃያ ሁለት ሺህ ሠራዊት ፈርቶ ተመለሰ። ምክንያቱም የምድያም ሠራዊት ከመቶ ሺህ በላይ ነበርና። አሁንም "አሥር ሺህው ብዙ ነው። ወደ ወንዝ አውርደህ ለያቸው።" አለው። ጌዴዎንም ወደ ወንዝ አውርዶ "ውኃ ጠጡ።" አላቸው።

ከአሥር ሺህው ሦስት መቶው በእጃቸው እየጠለፉ ሲጠጡ ዘጠኝ ሺህ ሰባ መቶ ያህል ሰራዊት ግን ተጐንብሰው በአፋቸው ጠጡ። በዚህም "ሌሎቹን (የተጐነበሱትን) አስመልሰህ በሦስት መቶው ተዋጋ።" ተባለ።

እርሱም ሦስት መቶውን ተከታዮቹን ይዞ መለከትና መብራት በሸክላ ይዞ በምድያም ሠራዊት አካባቢ አደረ። በዚያች ሌሊትም ጌዴዎንና ሠራዊቱ በምድያም መካከል ገብተው እንስራቸውን ሰበሩ።

መለከቱንም ነፉ። እንደ አንበሳም "ኃይል ዘእግዚአብሔር ኩዊናት ዘጌዴዎን - ኃይልን ከእግዚአብሔር ጦርን ከጌዴዎን" እያሉ ገጠሙ።

በድንጋጤ የተመቱት ምድያማውያንም እርስ በርሳቸው ተዋግተው በአንድ ሌሊት ብቻ መቶ ሁለት ሺህ ሠራዊት አለቀባቸው። ቀሪዎቹም ወገኖቻቸው አፈሩ። እስራኤል ግን በፈጣሪያቸው ኃይል ተፈሩ። ጌዴዎንም ለአርባ ዓመታት እስራኤልን አስተዳድሮ በዚህች ቀን ዐርፏል።
(መጽሐፈ መሳፍንት ከምዕራፍ ፮ - ፰)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአበው ቅዱሳን ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ እና አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ <3

ይህ ቅዱስ አባት ከሰማዕታት፣ ከጻድቃን፣ ከሊቃውንትና ከጳጳሳት ዝርዝር ውስጥ ይገኛል። በቤተ ክርስቲያንም ዐበይት ከሚባሉ አበው አንዱ ነው። ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሮማዊ ሲሆን ከክርስቲያን ወላጆቹ የተወለደው በዘመነ ሰማዕታት (በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ነው።

አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ቅዱሱ የታላቋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው። በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት፦
፩.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት፣
፪.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናትና
፫.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት።

ቅዱሱ ሦስቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ። ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት። መከራው በጣም ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ፣ ይጾሙ፣ ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር።

ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስን ጻድቃን የምንላቸው። በኋላ ግን ማኅደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኳ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ።

በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ። ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው። የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ።

በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ። በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር። መከራው ግን አለቀቃቸውም። ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው።

ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት። ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ አይሆንም።" አለችው። ሊያስፈራራት ሞከረ። ዓይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው።

አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው። እጅግ ስላፈረ አስገረፋት፣ አሰቃያት፣ ዓይኗንም አወጣ። በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት።

ወዲያው ደግሞ የቅዱስ ጐርጐርዮስ ማንነቱ በመታወቁ ይዘው አካሉ እስኪያልቅ ገረፉት። በእሳትም አቃጠሉት። በብዙ ስቃይም አሰቃዩት።

በመጨረሻ ግን ከነ ሕይወቱ እንዲቀበር ተወሰነበት። ወደ መጸዳጃ ቤት ወስደውም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት። ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ መተንፈሻ ቀዳዳን ሠራለት። አንዲት ሽማግሌ ክርስቲያንም በዚያች ቀዳዳ ቂጣ እየጣለችለት ለአሥራ አምስት ዓመታት ተቀብሮ ኖረ።

አካሉና አፈሩ ተጣበቀ። እርሱ ግን ፈጣሪውን እያመሰገነ ቆየ። ከነገር ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው።

የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ። የንጉሡ እኅት ስታለቅስ በራእይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን - ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም።" አላቸው። ወዲያውም በዚያች ሽማግሌ መሪነት ቆፍረው አወጡት።

አካሉንም እግዚአብሔር መለሰለት። ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም። ለአሥራ አምስት ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው። ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው።

ወደ ሰውነትም መልሶ መላ አርማንያን ወደ ክርስትና መለሰ። የንጉሡን እግር ግን የአውሬ አድርጐት ቀርቷል። በመጨረሻም ቅዱስ ጐርጐርዮስ የአርማንያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሹሞ ብዙ መጻሕፍትን ደረሰ። ከሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንትም አንዱ ሆኖ ተቆጠረ። ዛሬ ታኅሣሥ ፲፭ ቀን ዕረፍቱ ነው።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ እና አባ ሖር ገዳማዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ <3

አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልን እንዲያው በቀድሞው አጠራር ሠለስቱ ደቂቅ (ሦስቱ ሕፃናት) እንላቸዋለን እንጂ ለእኛስ በእድሜም፣ በጸጋም፣ በትሩፋትም አባቶቻችን ናቸው።

ቅዱሳኑ የወቅቱ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጆች ናቸው። ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ሲማርክ አብረው ተማርከው ባቢሎን ወርደዋል።

ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግሥት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር። ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ። ምንም እንኳ በቤተ መንግሥት ውስጥ ቢኖሩ ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ።

አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከእነርሱ የሚደርስ አልተገኘም። ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው። ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው።

ከነገር ሁሉ በኋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ። ናቡከደነጾር ስልሳ ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ ስገዱ ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው። ነበልባሉ ከጉድጓዱ ወደ ላይ አርባ ዘጠኝ ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም።

ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልአከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው። ከሆነው ነገር የተነሳም አሕዛብ አፈሩ። ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ።

ከዚያች ቀን በኋላ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል በአት አጽንተው በጾምና በጸሎት ተወስነው ኑረዋል። ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆኗል። ቅዱስ ዳንኤልና ናቡከደነጾር ተሯሩጠው ቢሄዱ ሦስቱም በአንድነት ዐርፈው ተገኝተዋል። ንጉሡ በእጅጉ ይወዳቸው ነበርና በወርቅ በተለበጠ ሳጥን ቀብሯቸዋል። ስሞት ከመካከላቸው ቅበሩኝ በማለቱ ዛሬ ድረስ ለበቁ አባቶች የአራቱ መቃብር ባቢሎን ውስጥ ይታያል።

ቅዱሳን አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል (ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጐ) ያረፉት ግንቦት ፲ ቀን ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ አምስት መቶ ዓመት በፊት ነው። ይህቺ ዕለት ደግሞ ናቡከደነጾር ወደ እሳት ሲጥላቸው መልአከ እግዚአብሔር እነርሱን ያዳነበት ቀን ናት።

አምላካቸው ከእሳት ባወጣቸው በዚህ ቀንም፦
"ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ
ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም።" የሚለውን ምስጋና ፈጣሪ ገልጾላቸው ደርሰውታል፤ በእሳቱ ውስጥ ሆነው ተናግረውታል።

ድርሰታቸው ሁለት ወገን ሲሆን ባለ ስድስት አንቀጹ ምስጋናቸው ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚያሳይ ነው። ሌላኛውና ሠላሳ ሦስት አንቀጾች ያሉት ምስጋናቸው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለሠላሳ ሦስት ዓመታት እንደሚመላለስ ያጠይቃል።

ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በኋላ (ማለትም ከክርስቶስ ልደት በአራት መቶ ዓመታት) ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ።

ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ "አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?" አለው። ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ። በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ። ሠለስቱ ደቂቅም "ወዳጃችን! ምን ሆንክ?" አሉት።

ቅዱሱም መልሶ "ወደ ግብጽ እንሒድ። አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋችኋል።" አላቸው። እነርሱም "ለቅዱስ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው። እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ። ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም። ለክብርህ ግን እንመጣለን። ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው።" ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት። ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርም መጥቶ መልእክቱን አደረሰ። በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን ቴዎፍሎስ፣ ቄርሎስ፣ ሐጺር ዮሐንስና ሌሎችም ከምዕመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ።

እጅግ የሚደነቅ ብርሃንም ከበባቸው። በብርሃኑ መካከል ሠለስቱ ደቂቅ ሲያልፉ በጐ መዓዛ ሸተተ። ሕዝቡም በደስታና በዝማሬ የቅዱሳኑን ቅዳሴ ቤት አክብሯል።

<3 አባ ሖር ገዳማዊ <3

በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ከጻድቃንም፣ ከሰማዕታትም አሉ። ከጻድቃኑ መካከል በተለይም ከታላላቆቹ አንዱ ቅዱስ አባ ሖር ነው። አባ ሖር በዘመነ ጻድቃን የነበረና በደግነቱ የሚታወቅ ክርስቲያን ነው።

በዓለም ያለውን በጐነት ሲፈጽም ድንግልናውን እንደ ጠበቀ ገዳም ገባ። በዚያም በአገልግሎት ተጠምዶ ዘመናትን አሳለፈ፤ ከዚያም መነኮሰ። ከመነኮሰ በኋላ ደግሞ አበውን በማገልገል፣ በጾም፣ በጸሎትና በበጐው ትሕርምት ሁሉ የተጠመደ ሆነ። ግራ ቀኝ የማይል ("ጽኑዕ ከመ ዓምድ ዘኢያንቀለቅል") እንዲሉ አበው ብርቱ ምሰሶ ሆነ።

ሰይጣንም አባ ሖርን በብዙ ጐዳና ፈተነው። ከእርሱ ጋር መታገል ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት በገሃድ ተገለጠለት። "አንተኮ የምታሸንፈኝ በአበው መካከል ስለ ሆንክ ነው። በበርሃ ብቻህን ባገኝህ ግን እጥልሃለሁ።" ሲል ተፈካከረው።

አባ ሖርም የዳዊትን መዝሙር እየዘመረ ጭው ወዳለ በርሃ ገባ። በዚያም ሰይጣን ታገለው። ግን ሊያሸንፈው አልቻለም። ምክንያቱም ኃያሉ እግዚአብሔር ከጻድቁ ጋር ነበርና። ሰይጣን እንደ ተሸነፈ ሲያውቅ እንደ ገና ሌላ ምክንያት ፈጠረ።

አሁንም በገሃድ ተገልጦ ተናገረው:: "በዚህ በበርሃ ማንም በሌለበት ብታሸንፈኝ ምኑ ይደንቃል! ወደ ከተማ ብትሔድ ግን አትችለኝም።" አለው። ቅዱስ ሖር ግን አሁንም ሰይጣንን ያሳፍር ዘንድ በፈጣሪው ኃይል ተመክቶ ወደ ዓለም ወጣ።

"እግዚአብሔር ያበርሕ ሊተ ወያድኅነኒ ምንትኑ ያፈርሃኒ - እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው። የሚያስፈራኝ ማነው!" (መዝ. ፳፮፥፩) ሲል ይጸልይ ነበር። በከተማም በነበረው ቆይታ አልባሌ ሰው መስሎ ደካሞችን ሲረዳ፣ ነዳያንን ሲንከባከብ፣ ለድሆች ውኃ ሲቀዳ፣ እንጨት ሲሰብር ይውልና ሌሊት እንደ ምሰሶ ተተክሎ ሲጸልይ ያድራል።

ሰይጣን በዚህም እንዳላሸነፈው ሲያውቅ ከሰዎች ጋር በሐሰት ሊያጣላው ሞከረ። ፈረስ ረግጦ የገደለውን አንድ ሕፃን ሲያይ ሰይጣን ሰው መስሎ ወደ አባ ሖር እየጠቆመ "እርሱ ነው ረግጦ የገደለው።" አላቸው። የሕፃኑ ወገኖች ቅዱሱን ሲይዙት አባ ሖር "ቆዩኝማ" ብሎ የሞተውን ሕፃን አንስቶ ታቀፈው።

ጸልዮ በመስቀል ምልክት አማተበበትና "እፍ" ቢልበት ሕፃኑ ከሞት ተነሳ። ለወላጆቹም ሰጣቸው። ይሕንን ድንቅ የተመለከቱ የእስክንድርያ ሰዎችም ይባርካቸው ዘንድ ሲጠጉት ተሰውሯቸው በርሃ ገባ። ውዳሴ ከንቱን ፈጽሞ ይጠላት ነበርና።

ጻድቁ አባ ሖር ቀሪ ዘመኑን በበርሃ አሳልፎ በዚህች ቀን በክብር ዐርፏል።

አምላከ ጻድቃን ቅዱሳን ከነደደ እሳት፣ ከዲያብሎስ ክፋትም ይሰውረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤልያስ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘጋዛ እና ቅድስት ቤርሳቤህ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ ቅዱስ ኤልያስ <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች። "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች። እርሱ ሰማይን የለጐመ፣ እሳትን ያዘነመ፣ ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና።
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እስራኤል (አሥሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ "ኢያስኑዩ" እናቱ ደግሞ "ቶና (ቶናህ)" ይባላሉ። በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማኅጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ።

ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል። ብርሃን የለበሱ አራት ሰዎች (መላእክት) መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው።

ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእስራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል። ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ንጽሕናንም የሚወድ እስራኤላዊ ነው።

ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት ዘጠኝ መቶ ዓመት በፊት) ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት፣ እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር። ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እስራኤል ገብተው ነበር።

ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር።

በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው። እርሱም "እሺ" ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ። ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ።

በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር። በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ፦
፩.ለድንግልና (ድንግል ነበርና)
፪.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና)
፫.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል።

መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን፣ በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን፣ በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም። በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእስራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት።

ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሃሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት። ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም፤ አልለውጥም።" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል።

ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም። የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል።" አላቸው። በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም።

በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች። ዘጠኝ መቶው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው። በእስራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ። የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ።

ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ፦
"ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል ዘቆምኩ ቅድሜሁ ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ።" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ።

ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ። እርሱን ቁራ ይመግበው፣ ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር። ይሔው ቢቀርበት ጸለየ። እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው። በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ።

ልጇ ሕፃኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት። ቀጥሎም ሰባት ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል። ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል።

ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል ስምንት መቶ ሃምሳ ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል። መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ ስምንት መቶ ሃምሳውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል።

ይህንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው። "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻየን ቀርቻለሁና።" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው።

ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል) ቀስቅሶ ታየው። እንጐቻ ባገልግል ውኃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው። በላ፣ ጠጣ፣ ተኛ። እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው። በሦስተኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ።" አለው።

ኤልያስም ለአርባ ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል። ከዚያ በኋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም። እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ ሁለት ጊዜ እሳትን አዝንሟል።

የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ።" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን።" አለው። ሦስት ጊዜ ከመንገድ ሊያስመልሰው ሞከረ። ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው። ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው። ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት።

ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሄኖክ ጋር ያርፋል።
ለተጨማሪ ንባብ (ከ፩ነገ. ፲፯ - ፪ነገ. ፪ እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ።)
ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ ንጉሥ አፄ ገብረ መስቀል እና ቅዱስ አካክዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጻድቅ አፄ ገብረ መስቀል <3

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ነገሮቿ የታደለች ናት። ከእነዚህም መካከል በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ብዙ ነገሥቶቿ (መሪዎቿ) ቅዱሳን (ጻድቃን) ናቸው። ለአንዲት ሃገር የመሪዎቿ ጥሩ ክርስቲያን መሆን እጅግ ወሳኝ ነው።

ባለፉት አርባ ዓመታት እንኳ የደረሰብንን የመንፈስ ዝለትና የሞራል ዝቅጠት ስንመለከት አንድም ችግሩ ከመሪዎቻችን እንደ ሆነ እናስተውላለን። የሃገራችንን ታሪክ ስንመለከት ግን በእሳትና በጦርነት መካከል ሆነው ለፈጣሪ የተገዙ ብዙ ነገሥታትን እናገኛለን።
እንደ ምሳሌም፦
፩.ንግሥተ ሳባ
፪.ቀዳማዊ ምኒልክ
፫.አብርሐ ወአጽብሐ
፬.ካሌብ
፭.ገብረ መስቀል
፮.ሐርቤ
፯.ላሊበላ
፰.ይምርሐ
፱.ነአኩቶ ለአብ
፲.ዳዊት
፲፩.ቴዎድሮስ ቀዳማዊ
፲፪.ዘርዓ ያዕቆብ
፲፫.በእደ ማርያም
፲፬.ናዖድ
፲፭.ልብነ ድንግል
፲፮.ገላውዴዎስ
፲፯.ዮሐንስ
፲፰.ኢያሱ ቀዳማዊና
፲፱.ተክለ ሃይማኖት መናኔ መንግሥትን እናገኛለን።

ከእነዚህ መሪዎቻችን መካከል እኩሉ መንግሥታቸውን ትተው በርሃ የገቡ ሲሆኑ እኩሉ ደግሞ በዙፋናቸው ላይ ሳሉ በጐ ሠርተው የተገኙ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ በጥፋታቸው ተጸጽተው ንስሐ የገቡ ናቸው።

ከነገሥት ጻድቃን መካከልም ይህች ዕለት የአፄ ገብረ መስቀል መታሰቢያ ናት። ጻድቁ ንጉሥ የአፄ ቅዱስ ካሌብ ልጅ ሲሆን በኢትዮጵያ የነገሠው በ፭፻፲፭ ዓ/ም ነው። ሲነግሥም እጅግ ወጣት ነበረ። ምክንያቱም አባቱ ካሌብ ከናግራን ጦርነት መልስ በመመነኑ በዙፋኑ የተቀመጠ ልጁ እርሱ ነበርና።

ከዚህ ቅዱስ የመጀመሪያ የምናደንቀው ስሙን ነው። የዛሬ አንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመት እንኳ በመስቀል የሚመኩ፣ ለመስቀል የሚገዙ መሪዎች መኖራቸው በዘመኑ የነበረውን የክርስትና ደረጃ ያሳያል። "ገብረ መስቀል" ማለት "የመስቀል አገልጋይ (ባሪያ)" ማለት ነውና።

አፄ ገብረ መስቀል በጐ ንጉሥ እንዲሆን የቅዱስ አባቱ ማንነት የረዳው ይመስላል። ያ ኃያል፣ ብርቱና ዓለም የፈራው አባቱ ሲጀመር በፍቅረ ክርስቶስና በድንግል እናቱ ፍቅር የተያዘ ደግ ሰው መሆኑ ሲቀጥል ደግሞ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መንግሥቱን እንደ ጨርቅ ትቶ ሲሔድ መመልከቱ እርሱንም ያው አድርጐታል።

እርሱም ከአባቱ እንዳየው በአክሱም ላይ በነገሠባቸው ዓመታት በጾምና በጸሎት፣ ፍትሕ ርትዕ ሳያጓድል፣ ድሃም ሳይበድል ይኖር ዘንድ ጥረት አድርጓል።

<3 አፄ መስቀል <3
ይህ ጻድቅ ንጉሥ ለእኛ ከተወልን ትሩፋቶቹ አንዱ በዓለ መስቀልን በአደባባይ ማስከበሩ ቅድሚያውን ይይዛል። በዓሉ መስከረም አካባቢ የሚደረግ ሲሆን "አፄ መስቀል" ይባላል።

ሕዝቡ፣ ካህናቱና መሣፍንቱ አድዬ አበባ እየዘነጠፉ ወደ ንጉሡ አደባባይ ይተማሉ። በዚያም በያሬድ ዝማሬ ለቅዱስ መስቀሉ ታላቅ በዓል ይከበራል። ይህ በዓል ይኼው ዛሬ በUNESCO ተመዝግቧል።

<3 ንጉሡና ቅዱስ ያሬድ <3
ሃገራችን ታላቁን ሰማያዊ ዜማ ያገኘችው በአፄ ገብረ መስቀል ዘመን ነው። ቅዱስ ያሬድ ከሰማይ ያገኘውን ማኅሌት ለመጀመሪያ ጊዜ በአክሱም ጽዮን፦
"ሃሌ ሉያ.....! ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ
ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ።" ብሎ ከሦስቱ ጸዋትወ ዜማ በአንዱ በአራራይ ሲያዜም ንጉሡ በዜማው ተመስጦ እየሮጠ ወደ ጽዮን ደርሷል።

ከዜማው ጥፍጥና (ጣዕም) የተነሳ ሁሉም ተደመሙ። ንጉሡም ከዚያች ቀን ጀምሮ ከቅዱስ ያሬድ የማይለይ ሆነ። ስብሐተ እግዚአብሔርንም ለብዙ ጊዜ ከቅዱሱ ሊቅ በጥዑም ዜማ ተቀምሞለት ተመገበ።

እንዲያውም አንዴ ሊቁ ሲያዜምለት ጻድቁ አፄ ገብረ መስቀል የቅዱስ ያሬድ እግር ላይ በትረ መንግሥቱን ተክሎበታል። ሁለቱም ከተመስጧቸው ሲነቁ ግን ንጉሡ ደንግጦ "ምን ልካስህ?" ቢለው "ወደ በርሃ አሰናብተኝ።" አለው።

አፄ ገብረ መስቀልም እያዘነ ፈቅዶለታል። ቅዱስ ያሬድም ከመሬት ክንድ ከፍ ብሎ ተንሳፎ የመሰናበቻ ምስጋናን፦
"ውዳሴ ወግናይ ለእመ አዶናይ ቅድስት ወብጽዕት....." ብሎ አንቀጸ ብርሃንን በሚጣፍጥ ዜማ ሰተት አድርጐ አደረሰ። ይህንን ሲሰማ ንጉሡ ፈጽሞ አለቀሰ።

እስከ መንገድ ድረስ ከሕዝቡና ሠራዊቱ ጋር ከሸኘው በኋላም ቅዱስ ያሬድ ጸለምት ላይ ሲደርስ በዜማ አሰምቶ "ሰላም ለኩልክሙ" አለ። አፄ ገብረ መስቀልና ሕዝቡም "ምስለ መንፈስከ" ብለውት ቀና ሲሉ ከዓይናቸው ተሰወረ። ንጉሡም በዘመኑ ማኅሌተ ሰማይ እንዲስፋፋ ብዙ ጥሯል።

<3 ንጉሡና ዘጠኙ ቅዱሳን <3
ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ወንጌልን እንዲሰብኩ፣ መጻሕፍትን እንዲተረጉሙና ገዳማዊ ሕይወትን እንዲያስፋፉ አፄ ገብረ መስቀል ትልቅ ጥረት አድርጓል።

በተለይ ከአባ ጰንጠሌዎንና አባ ሊቃኖስ ዘደብረ ቆናጽል ጋር ልዩ ቅርበት ነበረው። ዘወትርም ከእነርሱ ይባረክ ነበር። አቡነ አረጋዊንም በየጊዜው ይጐበኛቸው እንደ ነበር ይነገራል።

<3 ንጉሡና ታቦት <3
ልክ እንደ ቅዱስ መስቀሉ ሁሉ ታቦተ እግዚአብሔር በዑደት እንዲከበር ያደረገ ይህ ንጉሥ ነው ይባላል። መነሻው ደግሞ የደብረ ዳሕሞ መታነጽ ነው። አንድ ቀን አቡነ አረጋዊን ምን እንደሚሹ ቢጠይቃቸው "የድንግል እመቤታችን ማርያምን መቅደስ አንጽልኝ።" አሉት።

በደስታ አንቆጥቁጦ አነጻት። የምርቃቱ ዕለትም ንጉሡ፣ ጻድቁና ሊቁ (ማለትም ገብረ መስቀል፣ አረጋዊና ያሬድ) ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ተገኙ። በጊዜውም ታቦቱ ሲነግሥ ቅዱስ ያሬድ ባቀረበው ማኅሌታዊ ዜማና አበው ባደረጉት ዝማሬ ታቦቱ እየዞረ ታላቅ መንፈሳዊ ሐሴት ሆነ።

ደብረ ዳሞ ያኔ መወጣጫ ደረጃ ነበረው። ንጉሡና ቅዱስ ያሬድ ከበዓል ሲመለሱ በአቡነ አረጋዊ ጥያቄ መወጣጫው ተደርምሷል።

ጻድቁ "ዳሕምሞ (ደርምሰው)" ስላሉት ቦታው ዳሕሞ (ዳሞ) ተብሎ ቀርቷል። ቅዱሱ ንጉሥ አፄ ገብረ መስቀል ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጾ በዚህች ቀን ዐርፎ ተቀብሯል።

<3 ቅዱስ አካክዮስ <3

ይህ ቅዱስ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተነሱ ቅዱሳን ሊቃውንት አንዱ ነው። ተወልዶ ያደገው በቁስጥንጥንያ ሲሆን ትምሕርተ ሃይማኖትንም እዚያው ተምሯል። በ፬፻፶፩ ዓ/ም ጉባኤ ኬልቄዶን (ጉባኤ አብዳን) ሲጠራ እርሱም ጥሪ ደርሶት ነበር።

ነገር ግን ከመጀመሪያው ንጉሡ መርቅያንና ጳጳሱ ልዮን የተበተቡትን ሴራ ያውቅ ነበርና ሳይሔድ ቀረ። ጉባኤው ተጠናቆ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ መገደሉንና ሃይማኖት መካዱን (በተሰብሳቢዎቹ) ሲሰማ አዘነ።

ንጉሡን ረግሞ "ጌታ ሆይ! ከዚህ ከረከሰ ጉባኤ ያልደመርከኝ ተመስገን።" አለ። ከጥቂት ዓመታት በኋላም ምዕመናን ሃይማኖቱ የቀና መልካም እረኛ መሆኑን ሲረዱ የታላቂቱ ቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት።

ብዙ ድርሳናትንም ደረሰ። ወዲያው ግን ከመሪዎች ተዋሕዶን እንዲተው ትዕዛዝ መጣለት። እንቢ በማለቱም ስደት ተፈርዶበት በስደት ላይ ሳለ ዐርፏል።

አምላከ ነገሥት ጻድቃን ቅኑን መሪ በሁሉም ሥፍራ ያድለን። ከወዳጆቹ በረከትም አይለየን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአእላፍ ሰማዕታት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን ሰማዕታት <3

ቤተ ክርስቲያን ዛሬ (ኅዳር 29) የሁሉንም ሰማዕታት በዓል ታከብራለች። አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቅዱሱ ሊቅ) በመጽሐፈ ሰዓታት ሰማዕታትን፦
"መስተጋድላን ከዋክብት ብሩሃን
ማኅትዊሃ ለቤተ ክርስቲያን።" ይላቸዋል።

በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮም መንግሥት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር። የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግሥቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ፦ ፋሲለደስ፣
ገላውዴዎስ፣
ፊቅጦር፣
መቃርስ፣
አባዲር፣
ቴዎድሮስ (ሦስቱም)፣
አውሳብዮስ፣
ዮስጦስ፣
አቦሊና ሌሎቹም ነበሩ።

ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ፦
ማርታ፣
ሶፍያ፣
ኢራኢ፣
ታኡክልያና ሌሎቹም ነበሩ። ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር። ወቅቱ ከፋርስ፣ ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ (ሞተ)።

የሮም መንግሥትም ባዶ ሆነች። ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር። ግን እነርሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ።

በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪጳዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር። ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪጳዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው። ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም። የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው። ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው። ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች።

ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ። የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ። ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው። ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግሥት እንምረጥ።" አላቸው። ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ።

ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ ይጸልዩ ገቡ። ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር። ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው። ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ።

አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ - ቤተ ክርስቲያኖች ይዘጉ፤ ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ።" አለ። አጵሎን፣ አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ።

በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ።
ምድር በደም ታጠበች።
ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ።
እኩሉ ተገደለ።
እኩሉ ተቃጠለ።
እኩሉ ታሠረ።
እኩሉም ተሰደደ።

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም። ይልቁኑ እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው፣ እንደ ብዕር አጥንታቸው፣ እንደ ብራና ቆዳቸው ሆኖ ተጽፏል እንጂ። ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው።

ስለዚህም "ተጋዳዮች፣ የሚያበሩ ኮከቦች፣ የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለው እነርሱ እየቀለጡ አብርተዋል። ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ፻፶ እስከ ፫፻፲፪ ዓ/ም ድረስ ያለው ዘመን ነው።

በተለይ ግን ከ፪፻፸ዎቹ እስከ ፫፻፲፪ ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና። የአርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል። የሰማዕታት ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል፣ የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም።
(ማቴ. ፲፥፲፮ ፣ ማር. ፲፫፥፱ ፣ ሉቃ. ፲፪፥፬ ፣ ዮሐ. ፲፮፥፩ ፣ ሮሜ. ፰፥፴፭ ፣ ራእይ. ፪፥፱)

የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ነው።

<3 ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕት <3

ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው።
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት። ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ ፭ ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራእይ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት። በወለደችው ጊዜም በራእዩ መሠረት "ጴጥሮስ" አለችው።

ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተውት በሊቀ ጳጳሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ፣ ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ። ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ጴጥሮስን የግብጽ አሥራ ሰባተኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት።

ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር። ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር። ለአሥራ አራት ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ።

አርዮስን (ተማሪው ነበር) አውግዞ ለየው። ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ። ብዙ ተአምራትንም ሠራ። በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ጵጵስናው ላይ አልተቀመጠም። በኋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ።

ሕዝቡ "ከእርሱ በፊት እኛን ግደሉን።" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ጴጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ። በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ። ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ። ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ። ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአበው ቅዱሳን አባ ሊቃኖስ ወአባ ሰረባሞን ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ሊቃኖስ ዘደብረ ቆናጽል <3

ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮጵያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት። አባ ሊቃኖስ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው።

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው። በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር፦
፩.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ
፪.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግሥት) እና
፫.ገዳማዊ ሕይወት ነው።

አባ ሊቃኖስን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግሥት ነው። እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል። አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል።

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ጰንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ። ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ።

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮጵያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም። ስለዚህም በ፬፻፸ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮጵያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ።

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው። ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው። ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች። አባ ሊቃኖስና ስምንቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር።

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ። በወቅቱ በአቡነ ሰላማ፣ በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ ሊቃኖስ እንደ ገና አቀጣጠሉት።

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት። የካደውን እየመለሱ የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ።

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው። በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ ሊቃኖስ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማኅበር ነበር። በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም።

የነ አባ ሊቃኖስ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ። ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው። እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ።
ጰንጠሌዎን በጾማዕት፣
ገሪማ በመደራ፣
አረጋዊ በዳሞ፣
ጽሕማ በጸድያ፣
አባ ይምዓታ በገርዓልታ፣
ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ።

ልክ እንደ ባልንጀሮቻቸው ስምንቱ ቅዱሳን አባ ሊቃኖስም ከጻድቅነታቸው ባሻገር ለሃገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው። በነገራችን ላይ "አባ ሊቃኖስ" የመጀመሪያ ስማቸው ሳይሆን በትምህርታቸው (በእውቀታቸው) የተደመመ የአክሱም ሕዝብ ያወጣላቸው ስም ነው።

ሊቃኖስን "ሊቁ አባት" ማለት ነው ብለው የተረጐሙልን አበው አሉና።
ይሕስ በምን ይታወቃል ቢሉ፦
ዘጠኙ ቅዱሳን የማኅበር አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደየ ራሳቸው ገዳማት ሲሔዱ አባ ጰንጠሌዎንና አባ ሊቃኖስ እዚያው አክሱም አካባቢ በመቅረታቸው ይሏል።

ምክንያቱም ሕዝቡና ንጉሡ ሁለቱን አበው "አትራቁን" ብለው ለምነዋቸው ነበርና። በዚህም የተነሳ አባ ጰንጠሌዎን ከአክሱም ከተማ በላይ ባለች ጾማዕት (እንዳባ ጰንጠሌዎን) በሚሏት ተራራ ላይ ሲያርፉ አባ ሊቃኖስ ደግሞ ከዚያው ከጾማዕት አንድ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ደብረ ቆናጽል (የቀበሮዎች ተራራ) ላይ ዐርፈዋል።

በመካከላቸው ደግሞ የቅድስት ማርያም መግደላዊት ቤተ ክርስቲያን ይገኛል። አባ ሊቃኖስ በዓታቸውን ካደራጁና ገዳም ካነጹ በኋላ ደቀ መዛሙርትን አፈሩ፤ አስተማሩ።

እጅግ ከበዛው ተጋድሏቸው ባልተናነሰ መንገድ ለሃያ አንድ ዓመታት ያህል ከተራራው እየተነሱ ወንጌልን ሰብከዋል። መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች መጻሕፍትንም ከሱርስት (የሶርያ ልሳን) እና ከጽርዕ (የግሪክ ልሳን) ተርጉመዋል።

ሁልጊዜም ለአገልግሎት ሲወጡ በትረ ሙሴአቸውን አይለዩም ነበር። ሲሰብኩም ሲጸልዩም ተደግፈውባት ነበር። ታዲያ ከዘመን ብዛት የእጃቸው መዳፍ መነደሉን አበው፦
"ወበእሒዘ በትር ዘተሰቁረ ዕዱ" ሲሉ ይናገራሉ።

ዳግመኛ ማታ ማታ ለጸሎት እጆቻቸውን ሲያነሱ እንደ ፋና ቦግ ብለው ሲያበሩ ይታዩ ነበር። ጻድቁ አባ ሊቃኖስ ሥሙር በሆነ ሕይወታቸው በእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን በነገሥታቱና በሕዝቡ ዘንድም ሞገስን አግኝተዋል። ዛሬም ድረስ የአክሱም ሕዝብ ከልቡ ያከብራቸዋል።

አንድ ወቅትም ሳይገባን (በቸርነቱ) ሒደን ገዳማቸውን ተመልከተናል። አበው እንደሚሉት በደብረ ቆናጽል ላይ ያለው ደን የብዙ ሥውራን መኖሪያ ነው። ለአንድ ሺህ ዓመታት ተከብሮ ቢኖርም በ፲፱፻፳፰ ዓ/ም የጣልያን ወረራ ግን እንዳልነበረ ሆኖ ነበር።

ዛሬም በቀድሞ ገጽታው አይደለም። በገዳሙም ያገኘነው አንድ አባትን ነው። እጅግ ጣፋጭ የሆነ ራት አብልተው መርቀው ከሸኚ ጋር መልሰውናል።

ዓይናችን ግን ብዙ ነገሮችን ተመልክቶ አድንቋል። እንደ ሰማነውም ዛሬም መካነ ቅዱሳን በመሆኑ የጽዮን አገልጋዮችም ማረፊያ ነው። ጻድቁ አባ ሊቃኖስ ያረፉት ኅዳር ፳፰ ቀን ነው።

<3 ቅዱስ ሰረባሞን ሰማዕት <3

ቅዱሱ ሰው የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ሲሆን የቅዱሳን ሐዋርያት ዘመድ ነው። እርሱ ተወልዶ ያደገው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ነው። የዘር ሐረጉ ሲቆጠርም በቀጥታ ከሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስና ከስምዖን ቀለዮጳ ይደርሳል።

በልጅነቱ ያደገው በሥርዓተ ኦሪት ነው። ወጣት በሆነ ጊዜ ግን ፈጣሪ በሰጠው ሕሊና ተመራምሮ በክርስትና ለመኖር ወሰነ። የወቅቱን የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ሒዶ "አጥምቀኝ" ቢለው "ልጄ! ደስ ይለኝ ነበር። ግን ወገኖችህ አይሁድ ይገድሉኛል።" ሲል መለሰለት።

አክሎም "ወደ ግብጽ ሒደህ ብትጠመቅ የተሻለ ነው።" ስላለው ከኢየሩሳሌም ግብጽ ገባ። ግብጽ ደርሶ ከቅዱስ ቴዎናስ (አሥራ ስድስተኛ ፓትርያርክ) ክርስትናን ተምሮ ተጠመቀ። ቀጥሎም ወደ ገዳም ገብቶ ከመጀመሪያዎቹ መነኮሳት አንዱ ሆነ። ምናኔን ከአባ እንጦንስ ተምሮ ስም አጠራሩ ከፍ አለ።

በተጋድሎውና በንጽሕናው ስለ ወደዱትም የኒቅዮስ ጳጳስ አደረጉት። በዘመነ ሲመቱም ጣዖት አምልኮን ከአካባቢው አጥፍቷል። ስለዚህ ፈንታም በዲዮቅልጢያኖስ ተይዞ በዚህች ቀን ተገድሏል። ሲገደልም ልክ እንደ ቅድመ አያቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ፊቱ ያበራ ነበር።

አምላከ አበው ቅዱሳን መዓዛ ቅድስናቸውን ያሳድርብን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ያዕቆብ ዘግሙድ፣ አቡነ ተክለ ሐዋርያት እና ፊልሞና ሐዋርያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ <3

ይህ ስም በቤተ ክርስቲያን እጅግ ዝነኛና ታዋቂ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ ቁጥሩ ከዐበይት ሰማዕታት ሲሆን የፋርስ ኮከብ በመባልም ይታወቃል። ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ ("ሙ" ጠብቆ ይነበብ።) ተወልዶ ያደገው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ፋርስ (የአሁኗ ኢራን) ውስጥ ነው።

ያኔ ይህቺ ሃገር በአንድ ወገን ጠንካራ ክርስቲያኖች በሌላ ወገን ደግሞ ጣዖትን የሚያመልኩ ጨካኝ ነገሥታት ነበሩባት። ቅዱስ ያዕቆብም በክርስትና ትምህርት አድጐ ሚስት አገባ።

በዘመኑ ከነበረው ንጉሥ ሠክራድ ጋር በጣም ይዋደዱ ነበርና በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ሹም አድርጐ አስቀመጠው። በቤተ መንግሥት ውስጥ ምቾት የበዛበት ቅዱስ ያዕቆብ የጾምና የጸሎት ሕይወቱ እየቀዘቀዘ መጣ። በሒደትም ንጉሡ የሚለውን ሁሉ የሚፈጽም ሰው ሆነ።

አንድ ቀን ግን ሠክራድ ቅዱስ ያዕቆብን "ለእሳትና ለፀሐይ ስገድ። እነርሱንም አምልካቸው።" ሲል ጠየቀው። ከመጀመሪያ የተሸረሸረ ነገር ስለ ነበረ "እሺ! ደስ ይበለው።" ብሎ ለፀሐይ ሰገደ፤ እርሷንም አመለከ።

ይህቺ ዜና በዘመኑ ክርስቲያኖች ዘንድ ስትሰማ ታላቅ ሐዘንን ፈጠረች። ይልቁኑ እናቱ፣ እኅቱና ሚስቱ ይህንን ሲሰሙ አንጀታቸው አረረ። በዚህ ምክንያትም ሦስቱ ተሰብስበው አንድ ደብዳቤ ጽፈው ተፈራርመው ላኩለት።

የደብዳቤው ይዘት እንዲህ ይላል፦ "አንተ ክርስትናህን መካድህን ሰምተን አዘንን። በዚህም ምክንያት ከዚህ በኋላ በአካባቢህ መኖርን አንፈልግም። ለሞተልህ ለክርስቶስ ካልታመንሀ እኛ አንተን እንደ ልጅ፣ እንደ ወንድምና እንደ ባል ልናምንህ ይከብደናል።"

ይህንን ደብዳቤ ልከውለት እነርሱ አካባቢውን ለቀቁ። ቅዱስ ያዕቆብ ደብዳቤውን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ገብቶ ሲያነበው ደነገጠ። በዚህ ምድር ያሉት ዘመዶቹ እናቱ፣ አንዲት እኅቱና ሚስቱ ብቻ ናቸውና ውስጡ ተሸበረ። ተደፍቶም ምርር ብሎ አለቀሰ።

ሲመሽም በቤቱ ውስጥ ወደ ነበረው የቀድሞ የጸሎት ቦታ ሒዶ ተንበረከከ። ከንጉሡ ጋር በነበረው ያልተገባ ቅርርብ የፈጸመው ስህተት ሁሉ ቁልጭ ብሎ ታየው።

በጌታችን ፊት ቁሞም "ጌታ ሆይ! በምድር ካሉ የሥጋ ዘመዶቼ መለየት እንዲህ ካሸበረኝ ካንተ ፍቅር መለየትማ እንደ ምን ይጨንቅ ይሆን! በሰማያዊ ዙፋንህ ፊትስ እንዴት ብዬ እቆማለሁ!" ሲል አምርሮ አለቀሰ።

ሙሉውን ሌሊት በእንባና በጸሎት አድሮ በጠዋት ንስሐ ገባ። ከዚያች ቀን ጀምሮም ፍጹም በክርስቶስ ፍቅር ተጠመደ። ጾምና ጸሎትን ወዳጆቹ አድርጐ ከንጉሡ እልፍኝና አደባባይ ቀረ።

ይህንን ያወቀው ንጉሡ ሠክራድ ወደ እርሱ አስጠርቶ "ምን ሆነሃል? ስለ ምንስ በአምልኮ ከእኔ ተለየህ?" አለው። ቅዱስ ያዕቆብም መልሶ "የፈጠረኝን ክርስቶስን ትቼ አንተን በባዕድ አምልኮ አስደስትህ ዘንድ የሚገባ አይደለም።" ሲል ተናገረው።

ንጉሡ ቅዱሱን አስቀድሞ ሊያታልለው ሞከረ። እንቢ ሲለው ግን ደሙ በመሬት ላይ እስኪንጠፈጠፍ ድረስ አስገረፈው፤ አስደበደበው። ጭንቅ መከራዎችንም አሳየው። ቅዱስ ያዕቆብ ግን በፍቅረ ክርስቶስ ጸና።

በዚህ የተበሳጨው ንጉሡ እንዲቆራርጡት ግን ቶሎ እንዳይገሉት አዘዘ። ከዚያ ቀን በኋላ በቀን በቀን እየገቡ ከአካሉ ይቆርጡ ጀመር። ከጣቶቹ ተነስተው እጆቹን እስከ ክንዱ፣ እግሮቹን እስከ ታፋው ድረስ ቆረጡ። መሐል አካሉ (ወገቡና ራሱ) ብቻ ቀረ።

ይህ ሁሉ ሲሆን እርሱ ጌታን ይቀድሰው፣ ይጸልይም ነበር። "የወይን ግንድ ሆይ! እኔን ቅርንጫፍህ አድርገኝ።" ይለው ነበር።
(ዮሐ. ፲፭፥፭)
ከአካሉ እየቆረጡ የጣሉትም ሲቆጠር አርባ ሁለት ሆነ። አርባ ሦስተኛ ደግሞ የተረፈ አካሉ ነበር።

ያን ጊዜ ሊጸልይ ፈልጐ "ጌታ ሆይ!" ብሎ ጮኸ።
ይህንን አበው፦
"መንፈቀ አካሉ ጸለየ መዊቶ መንፈቁ" ብለው ገልጸውታል። ግማሽ አካሉ ሙቶ በቀረው ይጸልይ ነበርና ንጉሡም ከጩኸቱ በኋላ አንገቱን በሰይፍ ሲያስመታው ጌታችን ወርዶ ታቅፎ ወደ ሰማይ አሳረገው።

እናቱ፣ እኅቱና ሚስቱ ይህንን ሲሰሙ እያለቀሱና እየዘመሩ አካሉን ሰብስበው ገንዘውታል። ሽቱም አርከፍክፈውበታል። የዚህ ቅዱስ ገዳም (ታቦት) በኢትዮጵያ ታች አርማጭሆ በሚባለው በርሃ ውስጥ ይገኛል። ድንቅ የሆነ የበረከት ቦታም ነው።

<3 አባ ተክለ ሐዋርያት <3

ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሐዋርያት በአሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተነሱ ዐበይት ጻድቃን አንዱ ናቸው። በተለይ በጻድቁ ንጉሥ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በተባሕትዎም በትሩፋትም እጅግ የተደነቁ አባት ነበሩ።

ጻድቁ ሲጠሩ "ዘደብረ ጽሙና" አንዳንዴም "ዘገበርማ" እየተባሉ ነው። ምናልባትም በብዙ ቦታ ላይ ስለ ተጋደሉ በእነዚህ ቦታዎችም ላይ ስለ ነበሩ ሊሆን ይችላል እንደዚህ ተብለው የተጠሩት።

በብዛት የሚታወቀው ደግሞ በምድረ ሸዋ፣ ጐጃምና በምድረ አፋር አካባቢ በመኖራቸው ነው።
እስኪ አንዳንድ ነገሮቻቸውን እናንሳ፦
ጻድቁ ክርስቶስን በመከራው ይመስሉት ዘንድ ዘወትር ይተጉ ነበር።
አንዴ ሥጋ ወደሙ የተቀበለ አንድ ሰው በመንገድ ላይ ሲያስመልሰው ተመልከተው ሁሉ ተጸይፎ ሲሸሽ እሳቸው ግን ደስ እያላቸው ተመግበውታል። ምክንያቱም የእርሳቸው ዓይን የሚመለከተው የፈጣሪን ሥጋና ደም ነው። በዚህ ጊዜም ጌታ ከሰማይ ወርዶ በግንባራቸው ላይ ፀሐይን ሥሎባቸዋል። በዚህ ምክንያትም ፊታቸው ያበራ ነበር።
አንዴ ደግሞ በገዳማቸው አንድ ዶሮ ለእንግዳ ሊያርዱት ሲሉ "በአባ ተክለ ሐዋርያት ተማጽኛችኋለሁ!" በማለቱ ትተውታል።
በአፋር በርሃ አካባቢ ለአሥራ አራት ዓመታት ኑረዋል።

በአንድ በአት ውስጥም ለአርባ አንድ ዓመታት ኑረዋል። ጻድቁ አቡነ ተክለ ሐዋርያት እንዲህ ተመላልሰው በተወለዱ በሰባ አንድ ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈዋል።

<3 ቅዱስ ፊልሞና ሐዋርያ <3

ቅዱስ ፊልሞና ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሲሆን ብዙ ጊዜ "ጥዑመ - ቃል (አንደበቱ የሚጣፍጥ)" ተብሎ ይጠራል። በዘመነ ሐዋርያት በጣም ልጅ በመሆኑ እየተሯሯጠ ለአበው ይታዘዝ ነበር።

ጌታን አምኖ ተከትሎ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ተምሮ፣ ከቅዱስ መንፈሱ ነስቶ፣ ከቅዱስ እንድርያስ ጋር ለስብከት ወጥቷል። ሃገረ ስብከቱም ልዳ ነበረች። እርሱ ሲያነብ (ሲያስተምር) ሰው ሁሉ በተመስጦ ይሰማው ነበር። ሊገድሉት የመጡ ወታደሮች እንኳ በተደሞ መግደላቸውን ይረሱት ነበር።

አንዳንድ ቀን ደግሞ ወፎችና ርግቦች ያደምጡት፣ ያወሩትም ነበር። ይህቺ ቀን ለቅዱስ ፊልሞና ዕለተ ዕረፍቱ ናት።

አምላከ ቅዱሳን ብርሃናቸውን ያብራልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለተአምረ እግዝእትነ ማርያም፣ ቅዱስ ደቅስዮስ፣ ቅዱስ አንስጣስዮስ እና ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ተአምረ ማርያም <3

"ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል። መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው። ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ) ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል።

ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው። ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ - ከሐሌ ኩሉ - ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው።

እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል። በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ፣ መና ሲያዘንሙ፣ ውኃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት።) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ፣ እሳትን ሲያዘንሙ፣ ሙታንን ሲያስነሱ (፩ ነገሥት) እንደ ነበር ይታወቃል።

እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል። በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል።
(ማቴ. ፲፥፰ ፤ ፲፯፥፳ ፣ ማር. ፲፮፥፲፯ ፣ ሉቃ. ፲፥፲፯ ፣ ዮሐ. ፲፬፥፲፪)

እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል።
(ሐዋ. ፫፥፮ ፤ ፭፥፩ ፤ ፭፥፲፪ ፤ ፰፥፮ ፤ ፱፥፴፫-፵፫ ፣ ፲፬፥፰ ፤ ፲፱፥፲፩)

በተአምራት ብዛት ደግሞ ከጌታ ቀጥላ ድንግል እመ ብርሃን ትጠቀሳለች። ዛሬም የምናስበው የእርሷን ተአምራት ነው።

የእግዝእትነ ማርያም ሙሉ ሕይወቷ ተአምር ነው።
አበው "ድንግል ተአምራት ማድረግ የጀመረችው ገና ሳትወለድ ነው።" ሲሉ የሚጸንባቸው ሰዎች አሉ። ከአዳም ውድቀት በኋላ በእርሷ እንደሚድን "ሴቲቱ" (ዘፍ. ፫፥፲፭) በሚል ከተነገረው በኋላ ድንግል በብዙ ተአምራት (በምሳሌ) ተገልጣለች።

ለአብነት ያህልም እግዚአብሔር ኖኅን ከጥፋት ውኃ እንዲሁ ማዳን ሲችል ተአምራቱን በመርከብ ገለጠ።
(ዘፍ. ፯፥፩)
ለሚያስተውለው ያቺ መርከብ ድንግል ናት።
አብርሃም ይስሐቅን ሊሰዋ ሲል በተአምራት በግ በእፀ ሳቤቅ ተይዞ ተገኝቷል።
(ዘፍ. ፳፪፥፲፫)
ያዕቆብ በቤቴል ድንቅ መሰላልን ተመልክቷል። (ዘፍ. ፳፰፥፲፪)
ሙሴ በጽላቱ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል።
(ዘጸ. ፴፬፥፳፱ ፣ ዘሌ.፲፥፩)

የአሮን በትር ስትለመልም ድንቅ ተአምራቱ እመቤታችንን ያሳያል። ኢሳይያስ የድንግልን መጽነስ "ምልክት (ተአምር) ይሰጣችኋል።" ሲል ገልጾታል።
(ኢሳ. ፯፥፲፬)

በሐዲስ ኪዳንም የድንግል፦
ያለ በደል መጸነሷ፣
ንጽሕት ሆና መወለዷ፣
በቤተ መቅደስ ለአሥራ ሁለት ዓመታት ምድራዊ ምግብን አለመመገቧ፣
ያለ ወንድ ዘር መጸነሷ (ሉቃ. ፩፥፳፮)፣
ያለ ምጥ መውለዷ፣
በልደት ዕለት የታዩ ተአምራት (ሉቃ. ፪፥፩)፣
እናትም ድንግልም መሆኗ (ሕዝ. ፵፬፥፩) ሁሉ በራሱ ድንቅ ተአምር ነው።

ከዚህ ባለፈም በቃና ዘገሊላ ያደረገችውን ዓይነ ልቡናው ከታወረበት ሰው ውጪ ዓለም ያውቃል።
(ዮሐ. ፪፥፩)
ባለ ራእዩ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ "ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ። ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮቿ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።" ብሎ የእመቤታችን መገለጥ (መታየት) በራሱ ተአምር መሆኑን ነግሮናል።
(ራእይ ፲፪፥፩)

ድንግል እመቤታችን በሕይወተ ሥጋ ከሠራችው ተአምራት በበዛ መንገድ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ስትሠራ ኑራለች፤ እየሠራች ነው። ገናም ትቀጥላለች። ለሚያምናት ተአምራትን መሥራት ብቻ አይደለም ነፍሱንም ከሲዖል ታድነዋለች።

ሁሉን ቻይ ልጅ አላትና እርሷም ሁሉን ትችላለች። እንኳን የፈጣሪ እናት ድንግል ማርያም የክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያቱም "የሚሳናችሁ የለም።" ተብለዋል።
(ማቴ. ፲፯፥፳)

<3 ቅዱስ ደቅስዮስ <3

ይህ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ በዘመነ ጻድቃን አካባቢ እንደ ነበረ ይታመናል። ከምናኔ ሕይወቱ ባሻገር በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ የጥልጥልያ ሃገር ጳጳስም ነበር። ይህ ቅዱስ ሰው በእውነቱ ያስቀናል።

እመቤታችንን ሲወዳት መንጋትና መምሸቱ እንኳ አይታወቀውም ነበር። ፍቅሯ በደም ሥሮቹ ገብቶ በደስታ ያቃጥለው ነበርና ዘወትር እያመሰገናት አልጠግብ አለ። የሚያስደስትበትን ነገር ሲያስብ ደግሞ የተአምሯ ነገር ትዝ አለው።

ከዚያ በፊት የእመቤታችን ተአምሯ በየቦታው ይነገራል፣ ይጻፋል፣ ይሰበካል። ግን በአንድ ጥራዝ አልተያዘም ነበርና በሱባኤ፣ በፈጣሪው እርዳታ፣ በፍጹም ድካም የእመ ብርሃንን ተአምራት ሰብስቦ በአንድ ጠረዘውና ለአገልግሎት ቀረበ።

እርሷን ከመውደዱ የተነሳ ይህንን አድርጓልና እመ ብርሃን ወደ እርሱ ወረደች። "ወዳጄ ደቅስዮስ ደስ አሰኘኸኝ።" አለችው። መጽሐፉንም ተቀብላው ባረከችው። "አመሰግንሃለሁ" ብላውም ተሰወረችው።

በዚህ ጊዜ ቅዱሱ ሐሴትን አደረገ። (እመቤታችን ማየት እንዴት ያለ ሞገስ ይሆን!)
ቅዱስ ደቅስዮስ ግን ፍቅሯ እንደ እሳት ልቡን አቃጠለው። አሁንም ደስ ሊያሰኛት ምክንያትን ይሻ ነበር።

እመቤታችን ጌታን የጸነሰችበት በዓል (መጋቢት ፳፱) ሁሌም ዐቢይ ጾም ላይ እየዋለ ለማክበር አይመችም ነበርና ቅዱሱ ታኅሣሥ ፳፪ ቀን ሊያከብረው ወሰነ። በሃገሩ ያሉ ክርስቲያኖችን ጠርቶ ታላቅ በዓልን ለድንግል አከበረ።

ሕዝቡም ጸጋ በዝቶላቸው ስለ እመቤታችን ታላቅ ሐሴትን አደረጉ። በዚያች ሌሊትም እመ ብርሃን በሞገስ ወረደች። "ወዳጄ ደቅስዮስ! ዛሬም ፍጹም ደስ አሰኘኸኝ! እኔም ስለ ክብርህ ይህንን አመጣሁልህ።" ብላ ሰማያዊ ልብስና ዙፋን ሰጠችው።

ማንም እንዳይቀመጥበት ነግራው ባርካው ዐረገች። ከዚህች ዕለት በኋላ ቅዱስ ደቅስዮስ ፈጣሪውንና ድንግል እናቱን ሲያገለግል፣ ተአምሯን ሲሰበስብ፣ ምዕመናንን ሲመራ ኑሮ በዚህች ዕለት ዐርፏል። ከእርሱ በኋላ የተሾመው ጳጳስም በድፍረት በእርሱ ዙፋን ላይ በመቀመጡ መልአክ ቀስፎ ገሎታል።

የእመቤታችንን ተአምር መስማትና ማንበብ ያለውን ዋጋ የሚያውቅ ጠላት ሰይጣን ግን ዛሬም ድረስ ባሳታቸው ሰዎች አድሮ ተአምሯን ይቃወማል።
እኛ ግን ለእመቤታችን እንሰግዳለን! ተአምሯንም እንሰማለን! ጥቅማችንን እናውቃለንና!

ለመረጃ ያህልም፦
የእመቤታችንን ተአምር የሰበሰበ (ቅዱስ ደቅስዮስ)
የተአምሯን ሥርዓት ያዘጋጁ (ቅዱሳን አበው ማቴዎስ፣ ማርቆስና አብርሃም ሶርያዊ)
እሰግድ ለኪን የደረሰው (ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ)
የተአምሯን ሃሌታ (ቅዱስ ያሬድ)
የዘወትሩን መቅድም (ቅዱሳን ሊቃውንት) ናቸው።

ልመናዋ ክብሯ በእውነት ለዘላለሙ ይደርብን!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለኖላዊ ሔር ክርስቶስ፣ ለቅዱሳን በርናባስ ሐዋርያ እና አባ ይስሐቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ኖላዊ ሔር <3

እግዚአብሔር አዳምን በሰባት ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በኋላ ግን ንስሐ ስለ ገባ "ከአምስት ቀን ተኩል (ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው።

ከዚህ በኋላ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር ሱባኤ ይቆጠር ምሳሌም ይመሰል ገባ።

ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ። ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሳፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል። ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት /ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል።

ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል። እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህችን ዕለት "ኖላዊ ሔር" ብላ ታከብራለች። ይህንንም ለሳምንት ያህል ታዘክራለች። መሠረታዊ መነሻዋም (ዮሐ. ፲፥፩) ነው። "ኖላዊ" ማለት በቁሙ "እረኛ" ማለት ሲሆን "ሔር" ደግሞ "ቸር - ርኅሩኅ - አዛኝ" እንደ ማለት ነው።

ገጥመን ብንተረጉመው ደግሞ "ቸር እረኛ" የሚል ትርጉምን ይሰጠናል። ከአባታችን አዳም ስህተት በኋላ ተፈጥረው ከነበሩ ችግሮች አንዱ ቸር እረኛ ማጣት ነው። እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ ቸር እረኛ ሆኖ በገነት አሰማርቶት ነበር።

ኤዶም ገነት የለመለመች ፈሳሾች የሞሉባት መልካም መስክ ናትና። አባታችን ቅዱስ አዳም ደግሞ እንደ አቅሙ የጸጋ እረኝነት ተሰጥቶት ነበር። ድቀት ካገኘው በኋላ ግን ከነፍስ እረኛው ጋር ተጣልቶ ከመልካሟ መስክ ገነት ወጣ።

እርሷንና የነፍሱን እረኛ ሲሻም አለቀሰ። ተስፋ ድኅነት ሲሰጠውም ለልጆቹ ነገራቸው። ከዚያም በመንጋው ላይ በአዳም ሴት ተተካ። ከሴት ኄኖስ፣ ከኄኖስ፣ ቃይናን.....እያለ ከኖኅ ደረሰ።

ከኖኅም በሴም ከአብርሃም፣ ከአብርሃምም በይስሐቅና በያዕቆብ ወርዶ ከሙሴ ደረሰ። ከሙሴም በኢያሱ አልፎ ከነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ደረሰ። እነዚህ ሁሉ እረኞች ምንም እንኳ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በትጋት ቢሠሩም ሕዝቡን ከሲዖል ማዳን አልቻሉም።

ከሲዖል የሚያድን የነፍስ እረኛ ነውና ያን ጊዜ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የራሱን፣ የአባቶቹንና የልጆቹን ጩኸት ባንድ አድርጐ ጮኸላቸው። "ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምዕ - የእስራኤል እረኛ ሆይ ስማን!" አለ።
(መዝ. ፸፱፥፩)

ጩኸቱም ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ። ይህንን የሰማ ጌታም በጊዜው ከድንግል ማርያም ተወለደ። በየጥቂቱ አድጐ ቸር እረኝነቱን ገለጠ። መድኃኒታችን እንዳስተማረን እርሱ ቸር እረኛ ነው።

ከእርሱ በፊት የተነሱት ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ (ሐዋ. ፭፥፴፮ ፣ ዮሐ. ፲፥፰) ሐሰተኛ እረኞች ነበሩ። እርሱ ግን እውነተኛው የበጐች በር ነውና (ዮሐ. ፲፥፯) በእርሱ የሚገቡ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን ያገኛሉ።

እርሱ እውነተኛ እረኛ ነውና (ዮሐ. ፲፥፲፩) ለመንጋው ራሱን አሳልፎ ይሰጣል። በእስራኤል ባሕል እረኞች ከፊት መንጋው (በጐቹ) ከኋላ ሆነው ይሔዳሉና ገዳይ ቢመጣ መጀመሪያ የሚገድለው እረኛውን ነው።

መድኃኒታችን ክርስቶስ በሞቱ ሕይወትን፣ በመራቆቱ የጸጋ ልብስን፣ በውርደቱ ክብርን፣ በድካሙ ኃይልን ይሰጠን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። የማይሞት ንጉሥ ስለ መንጋው ሞተ። ሰማይን ከነግሡ ምድርንም ከነልብሱ የፈጠረ ጌታ (ዘፍ. ፩፥፩ ፣ ዮሐ. ፩፥፪) ስለ በጐቹ ይህንን ሁሉ ታግሦ ከሲዖል አዳነን።

በሚያርግ ጊዜም በእርሱ ፈንታ ባለ ሙሉ ሥልጣን እረኞችን፣ ሐዋርያትን (ዮሐ. ፳፩፥፲፭)፣ ሊቃነ ጳጳሳትን (ሐዋ. ፳፥፳፰)፣ ካህናትን (ማቴ. ፲፰፥፲፰) ሾመልን። እነርሱን እረኞች አሰኝቶ እርሱ "ሊቀ ኖሎት - የእረኞች አለቃ" ተባለ። እነርሱም እስከ ዓለም ፍጻም የክርስቶስን መንጋ ሊጠብቁ ሥልጣኑም፣ ኃላፊነቱም አለባቸው።
(ማቴ. ፳፰፥፲፱)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ሐጌ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ሐጌ ነቢይ <3

ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፣ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ።

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)
ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ።

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል።
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ።
(ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው። እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል።

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ። እናንተ በድካማቸው ገባችሁ።" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል።
(ዮሐ. ፬፥፴፮)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፤ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ።" እንዳለ ጌታ በወንጌል።
(ማቴ. ፲፫፥፲፮ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ።

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት፣ አራቱ ዐበይት ነቢያት፣ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ።

አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት፦
ቅዱስ አዳም አባታችን
ሴት
ሔኖስ
ቃይናን
መላልኤል
ያሬድ
ኄኖክ
ማቱሳላ
ላሜሕ
ኖኅ
አብርሃም
ይስሐቅ
ያዕቆብ
ሙሴና
ሳሙኤል ናቸው።

አራቱ ዐበይት ነቢያት፦
ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
ቅዱስ ኤርምያስ
ቅዱስ ሕዝቅኤልና
ቅዱስ ዳንኤል ናቸው።

አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት፦
ቅዱስ ሆሴዕ
አሞጽ
ሚክያስ
ዮናስ
ናሆም
አብድዩ
ሶፎንያስ
ሐጌ
ኢዩኤል
ዕንባቆም
ዘካርያስና
ሚልክያስ ናቸው።

ካልአን ነቢያት ደግሞ፦
እነ ኢያሱ
ሶምሶን
ዮፍታሔ
ጌዴዎን
ዳዊት
ሰሎሞን
ኤልያስና
ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው።

ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ።
የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እስራኤል)ና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ።

በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦
ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)፣
ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)፣
ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ።
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ።

ቅዱስ ሐጌ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፬፻፶ ዓ/ዓ አካባቢ ነው። "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው። አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸው።

"ሐጌ" ማለት መልአከ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መልእክተኛ) ማለት ነው። አንዳንዴም "በዓል" ተብሎ ይተረጐማል። ትውልዱ ከነገደ ጋድ ሲሆን አባቱ አግታ እናቱ ሲን ይባላሉ።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከደኃርት (ከኋለኛው ዘመን ነቢያት) አንዱ ነው ይባላል። ቁጥሩም ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ነው።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
እስራኤል ከተከፈለችበት ከመንግሥተ ሮብዓም (ከክርስቶስ ልደት ዘጠኝ መቶ ሠላሳ አንድ ዓመታት በፊት) በኋላ አሥሩ ነገድ "እስራኤል" ሁለቱ ነገድ "ይሁዳ" ተብለው በሰሜንና በደቡብ አቅጣጫ ተለያዩ። መናገሻቸውም ኢየሩሳሌምና ሰማርያ ሆኑ።

ከዕለት ዕለት ግን የሁሉም ኃጢአት እየበዛ በመሔዱ እግዚአብሔር አዘነባቸው። ለአሕዛብም አሳልፎ ሰጣቸው። አስቀድሞ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በሰባት መቶ ሃያ ሁለት ዓመት የአሦሩ ንጉሥ ስልምናሶር መጥቶ ሰማርያን አጠፋት። አሥሩን ነገድም በባርነት አሦር አወረዳቸው።

ከዚህ ትምህርት መውሰድ የተሳናቸው ሁለቱ ነገድም ሊገሰጹ አልቻሉምና ተመሳሳይ ዕጣ ደረሰባቸው። የእግዚአብሔርንና የነቢያቱን ድምጽ ይልቁኑ የኤርምያስን ምክር አልሰሙምና ከክርስቶስ ልደት አምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመታት በፊት ኃይለኛው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር መጣ።

የሚገድለውን ገድሎ ሕዝቡንም ማርኮ ወደ ፋርስ ባቢሎን ሲያወርዳቸው ኢየሩሳሌምን ምድረ በዳ አደረጋት።
(፪ነገ. ፳፭ )

እግዚአብሔርን የማይሰማ ሕዝብ ምን ጊዜም እጣ ፈንታው ይሔው ነው። በተለይ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቸርነት የበዛለት ሕዝብ እንዲህ አንገተ ደንዳና ሲሆን ይገርማል። በእርግጥ ዛሬ እስራኤል ያይደለ ሃገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ናትና ከመሰል መከራ ለመራቅ ድምጹን መስማት ያስፈልጋል።

ሕዝቡ ግን ፋርስ ባቢሎን ወርደው መከራን ሲቀበሉ ነቢያት ያሉት ሁሉ ሲፈጸምባቸው ተጸጸቱ። ፈጣሪም ተስፋ እንዳይቆርጡ በዚያው ዳንኤልን የመሰሉ ነቢያትን አስነሳላቸው። እነ ኤርምያስንም ከግብጽ ላከላቸው።

ሕዝቡም (በተለይ "ትሩፋን" የተባሉት) "እግዚአብሔር ሆይ! 'ወሰብዓ ዓም ኃሊቆ' ባልከው ቃልህ ሰባው ዘመን ሲፈጸም ወደ አባቶቻችን ርስት ብትመልሰን መቅደስህን እናንጻለን። በጐ ምግባርን እንይዛለን።" ሲሉ ተሳሉ።

ልመናን የሚሰማ ቸሩ ፈጣሪም እንደ ቃሉ ሰባው ዘመን ሲፈጸም እስራኤል በነ ኤርምያስ ባሮክና እና ሌሎችም አማካኝነት በኃይል፣ በድንቅና በተአምራት ከፋርስ ባቢሎን ወጡ። በድል ተጉዘውም ወደ ርስታቸው ገቡ።

የሰው ነገር አስቸጋሪ ነውና ከርስታቸው ከገቡ በኋላ ግን ስዕለታቸውን ሳይፈጽሙ ቀሩ። በዚህ ጊዜም እንደ ዘወትሩ ይገሥጻቸው ዘንድ እግዚአብሔር ነቢያቱን ሐጌን፣ ዘካርያስንና ሚልክያስን አስነሳቸው።

ሕዝቡ "እስመ ኢኮነ ጊዜሁ ለሐኒጽ - ለማነጽ ወቅቱ አልረዳንም።" እያሉ ቤተ መቅደሱ ሳይታነጽ ዘመናት አለፉ። የሚገርመው ግን ቤተ መቅደሱ ምድረ በዳ ሆኖ የራሳቸውን ቤት አሳምረው ያንጹ ነበር።

በዚህ ጊዜ በመካከላቸው የነበረው ቅዱስ ሐጌ ዘለፋቸው።
"እምጊዜሁ ለክሙ ከመ አንትሙ ትንበሩ ውስተ ቤት ጥፉር ወቤትየሰ ምዝቡር? - ቤቴ ፈርሶ ሳለ እናንተ ባማሩ ቤቶቻችሁ ልትኖሩ ጊዜው ነውን?" (ሐጌ. ፩፥፬) አላቸው።

አክሎም "ቃላችሁን አልፈጸማችሁምና በረከቴን ከእናንተ አርቃለሁ።" አላቸው። ተግሣጹን ከልብ የሰሙት ሕዝቡም በዘሩባቤል መሪነት አርባ ስድስት ዓመታት የፈጀውን ቤተ መቅደስን አንጸዋል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

አምላከ ቅዱሳን በመልአኩ ረድኤት ጠብቆ ለጻድቃኑ በረከት ያብቃን።

ታኅሣሥ ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ዮሐንስ ዘቡርልስ
፫.አቡነ ስነ ኢየሱስ ጻድቅ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፪.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፫.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም
፬.ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ

".....በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ። በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ፤ አስተማረኝም።....."
(ዳን ፱፥፳-፳፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን <3

ቅዱሱ በትውልዳቸው ግሪካዊ ቢሆኑም ሶርያ አካባቢ እንዳደጉ ይታመናል። በቀደመ ስማቸው ፍሬምናጦስ የሚባሉት አቡነ ሰላማ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በአደጋ ምክንያት ቢመስልም ውስጡ ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረበት።

በድንበር ጠባቂዎች ከባልንጀራቸው ኤዴስዮስ ጋር ተይዘው ወደ አክሱም የመጡት በንጉሥ ታዜር (አይዛና) እና በሚስቱ ሶፍያ (አሕየዋ) ዘመን ነው። ጊዜው በውል ባይታወቅም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው።

ፍሬምናጦስ ምንም የመጡበት ዓላማ ስብከተ ወንጌል ባይሆንም በአክሱም ቤተ መንግሥት አካባቢ ይሰብኩ ነበር። ያን ጊዜ በጃንደረባው ቅዱስ ባኮስ የተቀጣጠለው የክርስትና ችቦ ውስጥ ውስጡን በሃገሪቱ ነበረና ፍሬምናጦስ አልተቸገሩም። በተለይ ኢዛናና ሳይዛናን ከልጅነት ስላስተማሯቸው ነገሮች የተሳኩ ሆኑ።

ንጉሥ ታዜር እንደ ሞተ ሁለቱ ሕፃናት በመንበሩ ተቀመጡ። ፍሬምናጦስንም ወደ ግብጽ ጳጳስና ጥምቀት ከመጻሕፍት ጋር እንዲያመጣላቸው ላኩ። ሐዋርያዊ ቅዱስ አትናቴዎስም ፍሬምናጦስን "ሰላማ" ብሎ ሰይሞ በጵጵስና፣ በንዋየ ቅድሳትና በመጻሕፍት ሸልሞ መለሳቸው።

አቡነ ሰላማ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ ከነገሥታቱ ጀምረው ለሕዝቡ ጥምቀትን አደሉ። ኢዛናና ሳይዛናም አብርሃና አጽብሃ ተብለው ስማቸው ተደነገለ። ከዚያ በኋላ ድንቅ በሚሆን አገልግሎት ነገሥታቱ፣ ጳጳሱ ሰላማና ሊቀ ካህናቱ እንበረም ለክርስትና መስፋፋት በጋራ ሠርተዋል።

የአቡነ ሰላማ ትሩፋቶች፦
፩.ጵጵስናና ክህነትን ከእውነተኛ ምንጭ አምጥተዋል።
፪.ክርስትናና ጥምቀትን በሃገራችን አስፋፍተዋል።
፫.ቅዱሳት መጻሕፍትን ከውጭ ልሳኖች ተርጉመዋል።
፬.ገዳማዊ ሕይወትን ጀምረዋል።
፭.አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል።
፮.ግዕዝ ቋንቋን አሻሽለዋል።
ሀ.ከግራ ወደ ቀኝ እንዲፃፍ
ለ.እርባታ እንዲኖረው
ሐ.ከ"አበገደ" ወደ "ሀለሐመ" ቀይረዋል።

ባላቸው ንጹሕ የቅድስና ሕይወት ለሕዝቡ ምሳሌ ሆነዋ። "ወበእንተዝ ተሰይመ ከሣቴ ብርሃን" እንዲል በእነዚህ ምክንያቶች "ከሣቴ ብርሃን" (ብርሃንን የገለጠ) ሲባሉ ይኖራሉ። በመጨረሻም ከመልካሙ ገድል በኋላ በ፫፻፶፪ ዓ/ም ዐርፈው ተቀብረዋል። ቅዱሱ ለሃገራችን ጳጳስ ሆነው የተሾሙት በዚህች ዕለት ነው።

አምላከ አበው ቅዱሳን በመጽናታቸው ያጽናን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ታኅሣሥ ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
፪.ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
፫.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
፬.ቅዱስ ፊልሞና ባሕታዊ
፭.ቅዱስ ኢርቅላ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
፪.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
፫.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ)
፭.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ)

"የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ.....
መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ። በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ለሚሆን ልጄ ቲቶ።
ከእግዚአብሔርም አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።"
(ቲቶ ፩፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክም https://www.facebook.com/%E1%8C%88%E1%8B%B5%E1%88%88-%E1%89%85%E1%8B%B1%E1%88%B3%E1%8A%95-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994/ ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

አምላከ ቅዱስ ሉቃስ መካሪ ዘካሪ አባቶችን አያሳጣን። ከቅዱሱ በረከትም ያሳትፈን።

ታኅሣሥ ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ
፪.ቅዱስ ናትናኤል ጻማዊ
፫.ቅዱስ ማርቆስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ወቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
፫.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬.አባ ገሪማ ዘመደራ
፭.አባ ጰላሞን ፈላሢ
፮.አባ ለትጹን የዋህ
፯.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሊቅ
፰.ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ

"ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል። እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል።
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል።
በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።
ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ።
ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ።"
(መዝ ፺፩፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ማርያም እኅተ ሙሴ <3

ይህች እናት የሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴና የሊቀ ካህናቱ ቅዱስ አሮን ትልቅ እኅት ስትሆን ወላጆቿ እንበረምና ዮካብድ ይባላሉ። እስራኤል ከግብጽ ባርነት እንዲወጡ የእርሷን ያህል አስተዋጽኦ ያደረገች ሴት የለችም።

ከመነሻውም ቅዱስ ሙሴን የጠበቀች በሕግ በሥርዓት እንዲያድግ ከእናቱ ጋር ያገናኘች ወገኖቿ ከግብጽ ሲወጡም ሴቶችን የመራች እናት ናት። ወንድሞቿን ሙሴንና አሮንንም ታገለግላቸው ነበር። በተለይ እግዚአብሔር ባሕረ ኤርትራን የብስ ሲያደርጋት ከበሮን አንስታ "ንሴብሖ ለእግዚአብሔር" ብላ ፈጣሪዋን አመስግናለች።
(ዘጸ. ፲፭፥፳)

አንድ ጊዜም ሙሴን "ኢትዮጵያዊቷን ሲፓራን ለምን አገባህ።" በሚል ስለ ተናገረችው እግዚአብሔር ተቆጥቶ በለምጽ መቷታል።
(ዘኁ. ፲፪፥፩)
ቆይቶም በቅዱሱ ምልጃ ምሯታል። ማርያም በመንገድ ሳሉ ወደ ርስት ሳይደርሱ ዐርፋ ተቀብራለች።
(ዘኁ. ፳፥፩)

አምላከ ኃያላን መንፈሳዊ ኃይልን ልኮ ጠላትን ያድክምልን። ከወዳጆቹ በረከትም ይክፈለን።

ታኅሣሥ ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጌዴዎን ኃያል
፪.ማርያም እኅተ ሙሴ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፭.ቅዱስ አኖሬዎስ ጻድቅ
፮.አባ ዳንኤል ገዳማዊ
፯.አባ አቡናፍር ገዳማዊ

"እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ። ጽድቅንም አደረጉ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፪-፴፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን <3

ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው። በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ የኤዎስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም።

ጻድቁ በ፲፪፻፷፭ ዓ.ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው ክርስቶስ ሞዐና ሥነ ሕይወት ይባላሉ። የጻድቁ የመጀመሪያ ስም "ማዕቀበ እግዚእ" (ለጌታ የተጠበቀ) ነው። ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በኋላ ነው።

ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም። ከመምህር ዘንድ ገብተው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው፣ ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ። በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ (ፈጣን) በመሆናቸውም የዘመኑ አበው "ዳግማዊ እስጢፋኖስ" እያሉ ይጠሯቸው ነበር።

ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ። እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ።

በዘባነ ኪሩብ በግርማው ቢያዩት ደነገጡ። ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ! ገና ከእናትህ ማኅጸን መርጬሃለሁ። ከኢትዮጵያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ። "ዘኪያከ ሰምዐ ኪያየ ሰምዐ..... አንተን የሰማ እኔን ሰማ። አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ።" ብሏቸው ባርኳቸው ዐረገ።

ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ። ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ። በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ ያመነውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እያጸኑ ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ።

አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል። በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል አፍርተዋል።

አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት ቀዳሚት ሰንበት እንዳትናቅ (እንድትከበር) ባደረጉት ጥረት ነው። ደግሞም ተሳክቶላቸዋል። ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን ሁለቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው።

አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሁለት ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በእግራቸው ተጉዘዋል። መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም። ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ። እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና።

በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ። እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ።

በመንገድም ወደ ባሕረ ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ። ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን (ኩታቸውን) አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት። በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት።

ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ። ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ። ሚካኤል በቀኝ ገብርኤልም በግራ ቆሙ። ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው ይተረጉሙላቸው ገቡ።

በመካከል ግን አንዱ (የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት።) በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ። በኋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው ከሞት አስነስተውታል። በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ - ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ።

አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በተወለዱ በሰማንያ ዓመታቸው በ፲፫፻፵፭ ዓ.ም ዐርፈዋል። በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ መርምሕናም ተቀብረዋል። በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብጽና አርማንያ ይከብራሉ። ዛሬ ጻድቁ ማዕበሉን የተሻገሩበት መታሰቢያ ቀን ነው።

አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል በምሕረቱ ይጐብኘን። ከበረከታቸውም ያሳትፈን።

ታኅሣሥ ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሊቅ (ዘአርማንያ)
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
፫.ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ
፬.አባ ይምላህ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፪.ቅድስት እንባ መሪና
፫.ቅድስት ክርስጢና
፬.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፭.ቅዱስ ቂርቆስ ሰማዕት
፮.ብጽዕት ኢየሉጣ ሰማዕት

"ጻድቃን ጮሁ። እግዚአብሔርም ሰማቸው። ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።
እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው።
መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።
የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው።
እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል።"
(መዝ ፴፫፥፲፯-፳)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ታኅሣሥ ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ (አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል)
፪.አባ ሖር ጻድቅ
፫.ቅዱስ አውካቲዎስ ሰማዕት
፬.አባ አንበስ ሰማዕት
፭.ሰባት ሺህ ሠላሳ ሦስት ሰማዕታት (የቅዱስ ፋሲለደስ ማኅበር)
፮.ቅዱስ ናትናኤል መነኮስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)
፪.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
፭.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
፮.ሊቁ አባ ሕርያቆስ
፯.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ

"ናቡከደነፆርም መልሶ 'መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባርያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ።' "
(ዳን ፫፥፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ጴጥሮስ ዘጋዛ <3

ይህ ቅዱስ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በታናሽ እስያ አካባቢ የተወለደ ሲሆን የክቡራኑ የመሣፍንት ልጅ ነው። በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድጐ የቁስጥንጥንያ ንጉሥ ትንሹ ቴዎዶስዮስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ወሰደው።

በዚያም "አገረ ገዥ ላድርግህ።" ብሎ ቢጠይቀው "ትንሽ ቆየኝማ።" ብሎት ጠፍቶ በርሃ ገብቶ መነኮሰ። ቅዱስ ጴጥሮስ በምንኩስና ሲጋደል ካለበት በርሃ መጥተው በግድ ወስደው የጋዛ (አሁን የፍልስጤምና እስራኤል ድንበር) ጳጳስ አደረጉት።

ከደግነቱ የተነሳም በቅዳሴ ጊዜ ሥጋ ወደሙ ሲለወጥ ያየው ነበር። መላእክትም ያጫውቱት ነበር። ሕዝቡ ሲያጠፉ በየዋሕነት ዝም ቢላቸውም ቅዱስ መልአክ ገሥጾታል።

የፋርስ ነገሥታት አጽመ ሰማዕታትን ሲያቃጥሉም እርሱ የቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድን አጽም ይዞ ተሰዷል። ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑሮም በዚህች ቀን ዐርፏል።

<3 ቅድስት ቤርሳቤህ <3

ይህቺ እናት አስቀድማ የኦርዮ ሚስት ቀጥሎ ደግሞ የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሚስትና የሰሎሞን እናት ለመሆን በቅታለች። ቁጥሯ ከደጋግ እናቶቻችን ሲሆን የድንግል ማርያም ቅድመ አያትም ናት። አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ ስሟን "ቤትስባ (ቤተ ሳባ)" ትውልዷንም ከኢትዮጵያ ያደርጉታል።

አምላከ ኤልያስ በምልጃው ለሃገራችንና ለሕዝቧ ርኅራኄውን ይላክልን። ከቅዱሳኑም በረከት ይክፈለን።

ታኅሣሥ ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኤልያስ ርዕሰ ነቢያት
፪.ቅዱስ ጴጥሮስ ዘጋዛ
፫.ቅድስት ቤርሳቤህ (ቤትስባ)
፬.ናቡቴ ኢይዝራኤላዊ
፭.አባ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
፭.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት

"ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝኩትን የባሪያየን የሙሴን ሕግ አስቡ። እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።"
(ሚል ፬፥፬-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አፄ ገብረ መስቀል ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፪.ቅዱስ አካክዮስ ሊቅ
፫.ቅዱሳን ቆዝሞስ ወድምያኖስ
፬.ቅዱስ አናንዮስ ዘዓምድ
፭.አባ መርቆሬዎስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፫.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፭.አባ ሣሉሲ ክቡር ጻድቅ

"አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል። በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል።
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው። የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም።
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና። ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ።
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም። ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ።
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው።"
(መዝ ፳፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮም <3

የዚህ ቅዱስ ሐዋርያ ስሙ እንደ ምን ያምር! እንደ ምንስ ይከብር! ለቤተ ክርስቲያን ትልቁ ድልድዩዋ ነውና። ቅዱስ ቀሌምንጦስ የቅዱስ ቀውስጦስና የቅድስት አክሮስያ ልጅ ሲሆን ወንድምም ነበረው።

አባትና እናቱም የሮም መሳፍንት፣ በስብከተ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት ያመኑ፣ ገንዘባቸውን በምጽዋት የጨረሱ የመጀመሪያዎቹ የሮም ክርስቲያኖች ናቸው። ልጆቻቸው (ቀሌምንጦስና ወንድሙ) በመርዝ ቢሞቱባቸው በአምላከ ጴጥሮስ ተማጽነው ተነስተውላቸዋል።

አንድ ጊዜ ቀውስጦስ በሌለበት አንድ ሰው አክሮስያን ስላስቸገራት ልጆቿን ይዛ ተሰዳለች። በመንገድም መርከባቸው ተሰብሮ ቅዱስ ቀሌምንጦስ በስባሪው ግብጽ ደርሷል። በዚያም ቅዱስ ጴጥሮስን አግኝቶት የሊቀ ሐዋርያት ደቀ መዝሙሩ ሆኗል።

ቅዱስ ጴጥሮስንም ተከትሎ ለአገልግሎት ብዙ አሕጉራትን ዙሯል። ብዙ ምሥጢራትንም ተካፍሏል። የቅዱሳን ሐዋርያትን ዜናም ከቅዱስ ሉቃስ (ግብረ ሐዋርያት) ቀጥሎ የጻፈ እርሱ ነው።

ቅዱሳን ሐዋርያት ሙሉ ቀኖናቸውን ለቅዱስ ቀሌምንጦስ ሲሰጡት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ሰብአ ሰገል ለክርስቶስ ያመጡትን ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤውን አስረክቦታል። በተለይ ሁሉም ሐዋርያት ባረፉ ጊዜ እርሱ ቤተ ክርስቲያንን ተረከበ። በሮም ሁለተኛው ፓትርያርክ ሆነ።

በጊዜው መጽሐፈ ቅዳሴ ባለ መደራጀቱ ሥጋውን ደሙን ሲፈትቱ ፈጣሪ እንዳመለከታቸው ይጸልዩ ነበር። ቅዱሱ ግን የጌታንና የሐዋርያትን ቅዳሴ ዛሬ በምናየው መንገድ አደራጅቶ ጽፎታል። በስሙ የሚጠራና "ቀሌምንጦስ" የሚባል መጽሐፉም (ስምንት ክፍሎች አሉት።) ከሰማንያ አንዱ (አሥራው) መጻሕፍት ተቆጥሮለታል።

ቅዱሱ ሐዋርያ እንዲህ ሲመላለስ ኖሮ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በጠራብሎስ እጅ ወደቀ። ንጉሡም "ክርስትናን አስተምረሃል።" በሚል ብዙ አሰቃይቶ ከትልቅ ድንጋይ ጋር አስሮ ባሕር ውስጥ አስጥሞታል፤ በዚህም ዐርፏል።

ሁሌ ግን በዓመት በዓመት ባሕሩ እየተከፈለላቸው ምዕመናን እየገቡ ከቅዱስ አካሉ ይባረካሉ። ቅዱሱን ብዙ ጊዜ "ቀሌምንጦስ ዘሮም" የምንለው "ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ" የሚባል መናፍቅ ስላለ ከእርሱ ለመለየት ነው።
የቅዱሱ ክብር በእውነት ታላቅ ነው!

አምላከ ሐዋርያት ወሰማዕት በመከራቸው ከመከራ ይሰውረን። በረከታቸውንም ያብዛልን።

ኅዳር ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ሰማዕታተ ክርስቶስ (ሁሉም)
፪.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሐዋርያ (ዘሮም)

ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
፪.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፫.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊት
፬.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ
፭.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ። የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ። ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት። የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች አደረጉ። የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት። ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ። የሚቀብራቸውም አጡ።"
(መዝ ፸፰፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ሊቃኖስ ጻድቅ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)
፪.ቅዱስ ሰረባሞን ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
፮.ቅዱስ አባዲርና ቅድስት ኢራኢ

"ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፱-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፪.አቡነ ተክለ ሐዋርያት ጻድቅ
፫.ቅዱስ ፊልሞና ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሰማዕት
፭.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት
፮.አባ ገብረ ዮሐንስ ጻድቅ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
፪.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
፫.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፬.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፭.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፮.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

"ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ። በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?
.....እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን። ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።"
(፩ቆሮ ፲፥፲፬-፲፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ <3

እኒህ ጻድቅ ደግሞ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው። "ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው። ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል።

ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች። በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ፣ ምጽዋትን ወዳጅ፣ ቡርክት ሴት ነበረች። እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር።

ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማኅጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ።" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች። ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ ሰባት አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች።

ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕፃን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ። ይህችን ጸሎት በሕፃን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?" እያሉ ይሰግዱ ነበር።

የአምስት ዓመት ሕፃን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል። ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ። ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል። የፈጣሪውን ስም ያቃለለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል።

ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ትምህርት ቤት ገብተው መጻሕፍትን አጥንተው መንነዋል። በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በኋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም።
ባሕር ውስጥ ሰጥመው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ።
በየቀኑ አራቱን ወንጌልና መቶ ሃምሳውን መዝሙረ ዳዊት ይጸልያሉ። (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው።)
በአርባ ቀናት ቀጥሎም በሰማንያ ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ።
ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው።
በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ። (ካህን ናቸውና)
ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ፤ ክቡር ደሙን ይጠጣሉ።
በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን፣ መከፋትን አላሳደሩም።

በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር። ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በኋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ አላቸው።
"ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ፣
ስለ ምናኔህ፣
ስለ ተባረከ ምንኩስናህ፣
ስለ ንጹሕ ድንግልናህ፣
ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ፣
ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ፣
ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ ሰባት አክሊላትን እሰጥሃለሁ።"

"በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን አምስት መቶ የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ። በስምህ የሚለምኑ፣ በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ 'አማንየ! በርእስየ!' ብዬሃለሁ።" አላቸው።

ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው። ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ ሦስት ጊዜ ሳማቸው። ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፤ በዝማሬም ወሰዷት።

<3 የናግራን ሰማዕታት <3

በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ናግራን (የአሁኗ የመን) የክርስቲያኖች ሃገር ነበረች። የሳባ ግዛትን የእኛ ነገሥታት ሲተዋት የተተካው ፊንሐስ ደግሞ ጨካኝ አይሁዳዊ ነበርና ናግራንን ሊያጠፋት ተመኘ። ቀጥሎም "ሃገራችሁን ልጐብኝ።" ብሎ በማታለል ገባ።

ወዲያውም ሕዝቡንና ካህናትን ሰብስቦ "ክርስቶስን ካዱ።" አላቸው። ጽኑ ክርስቲያኖች ግን "አይደረግም!" አሉት። እርሱም ሊያስፈራራቸው አስቦ አራት ሺህ ያህል ካህናት፣ ዲያቆናትና ምሑራንን ጨፈጨፋቸው።

ይህንን አድርጐ "አሁንሳ?" አላቸው። ሕዝቡ ግን አሁንም "ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን የለም።" አሉት።
(ሮሜ. ፰፥፭)
ጨካኙ ፊንሐስም እንደ ገና ከሕዝቡ መካከል ከአራት ሺህ አንድ መቶ በላይ የሚሆኑትን ጨፈጨፈ።

ታላቁን ቅዱስ ሒሩትንም (የሕዝቡ መሪ ነው።) ብዙ አሰቃይቶ ሰየፈው። ሚስቱን ቅድስት ድማሕንም ሁለት ሴት ልጆቿን ሰይፈው የልጆቿን ደም አጠጧት፤ ከዚያም ሰየፏት። ይህንን የተመለከቱ የናግራን ክርስቲያኖች ግን ስለ መፍራት ፈንታ በፈቃዳቸው እየተሯሯጡ ወደ እሳትና ሰይፍ ተሽቀዳደሙ።

ከተማዋም እየነደደችና ደም እየፈሰሰባት ለአርባ ቀናት ቆየች። ይህንን የሰማው ቅዱሱ አፄ ካሌብም ደርሶ የተረፉትን ሲታደግ ፊንሐስን ከነ ወታደሮቹ አጥፍቶታል።

አምላከ አበው ወሰማዕት ጣዕመ ፍቅራቸውን፣ ክብራቸውን፣ ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን።

ኅዳር ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ንጹሕ
፫.ቅድስት ዮስቴና ቡርክት
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.ቅዱስ ሒሩት አረጋዊ
፮.ቅዱሳን ቢላርያኖስ፣ ኪልቅያና ታቱስብያ (ሰማዕታት)
፯.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘደሴተ ሰንሲላ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና።ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል።.....
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…
Subscribe to a channel