እንኳን ለቅዱሳን ሊቃውንት አባ ሕርያቆስና አባ ሳዊሮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ሊቁ አባ ሕርያቆስ <3
ክርስቲያን ሆኖ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ሁሉ ይህንን አባት ያውቀዋል። አባ ሕርያቆስ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ ሲሆን አካባቢው ብህንሳ (ንሒሳ) ይባላል። ይህቺ ቦታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጨምሮ በርካታ ቅዱሳንን ያፈራች ናት።
አባ ሕርያቆስን በዚህ ዘመን ነበረ ብዬ ትክክለኛውን ዓ.ም ለመናገር ይከብደኛል። ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት መረዳት እንደሚቻለው ግን የነበረበት ዘመን አራተኛው ወይ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ሆነ መገመት ይቻላል።
ቅዱሱ በዘመኑ የተለየ ማንነት የነበረው ሰው ነው። ገና ከልጅነቱ እመ ብርሃንን የሚወዳት በመሆኑ ቅን፣ የዋህና ገራገር ነበረ። መቼም እመቤታችንን ይወዳል ሲባል እንደ ዘመኑ በአፍ ብቻ እንዳይመስለን። ቀንና ሌሊት ለፍቅሯ የሚተጋ ማዕበለ ፍቅሯ የሚያማታው ሰው ነበር እንጂ።
የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ስም ሲጠራ ምስጥ ብሎ ልቡናው ይሰወርበት ነበር። ዘወትር የእርሷን ፍቅር ከማሰብ በቀር ሌላ ሥራ አልነበረውም። የልጅነት ጊዜው ሲያልፍም ድንግልንና ቸር ልጇን ያገለግል ዘንድ መነነ።
ዘመኑ ዘመነ ሊቃውንት እንደ መሆኑ ሁሉም ለትምህርት ሲተጉ እርሱ ግን ለጸሎትና ለደግነት ብቻ ነበር የሚተጋው። ከትምህርት ወገንም የሰሞን ጓዞችን፣ አንዳንድ ቅዳሴያትንና የዳዊትን መዝሙር ተምሮ ነበር።
በተለይ ግን የዳዊትን መዝሙር እየጣፈጠው መላልሶ መላልሶ ያመሰግንበት ነበር። ከዳዊት መዝሙር መካከል ደግሞ መዝሙር አርባ አራትን ፈጽሞ ይወዳት ነበር። ይህቺ ጥቅስ የምትጀምረው "ጐስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" ብላ ነው። የውስጧ ምሥጢርም ስለ ድንግል ማርያምና ስለ ክርስቶስ ነው።
አባ ሕርያቆስ ይህቺን መዝሙር በቃሉ አጥንቶ ቁሞም ተቀምጦም፣ ተኝቶም ተነስቶም ያለ ማቋረጥ ይላት ነበር። እየጣፈጠችው "ልቡናዬ በጐ ነገርን አወጣ።" እያለ ይዘምር ነበር። በወቅቱ ታዲያ የብህንሳ ኤጲስ ቆጶስ በማረፉ ምትክ ሲያፈላልጉ መንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስን መረጠ።
ምንም አለመማሩ ቢያሰጋቸውም "በጸሎቱና በደግነቱ ሃገር ይጠብቃል።" ብለው ሾሙት። ነገር ግን ምንም በሥልጣን የበላያቸው ቢሆን ተማርን የሚሉ ሰዎች ይጠሉት ይንቁትም ነበር። እርሱ ግን እንደ ጠሉኝ ልጥላቸው፣ እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር ያገለግል ነበር።
አንድ ቀን ታዲያ መንገድ ይወጣል። በበርሃ ብቻውን እየተራመደ "ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" እያለ እየዘመረ ተመሥጦ ቢመጣበት መንገድ ሳተ። እርሱ በምስጋናው ሲደሰት እግሩ ግን ከገደል ጫፍ ደርሶ ነበር። ገደሉን ልብ አላለውም ነበርና ሳይታወቀው ወደ ገደሉ ውስጥ ተወረወረ።
በዚህ ጊዜ ደንግጦ ቢመለከት እጅግ ጥልቅ በሆነ ገደል ውስጥ ራሱን አገኘው። ነገር ግን አንድም አካሉ አልተነካም፤ ልብሱም አልቆሸሸም። ለራሱ ተገርሞ ዙሪያ ገባውን ሲመለከት እርሱ ቁጭ ያለበት ብርሃንን የተሞላ የልብስ ዘርፍ ነበር።
"እመ ብርሃን!" ብሎ ሲጮህ የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነች እመቤታችን ከፊቱ ቁማ ታየችው። እመ አምላክን በገሃድ ቢያያት እንደ እንቦሳ ዘለለ።
የሚገርመው ደግሞ የተቀመጠበት የድንግል ማርያም የቀሚሷ ዘርፍ ነበር። እመቤታችን አነጋገረችው፤ ባረከችው። ፍቅሯ ቢመስጠው ከሰው ሳይገናኝ ምግብም ሳይበላ እዚያው ገደሉ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል በተመስጦ ቆይቷል።
በኋላ እመ ብርሃን መጥታ ከገደሉ አውጥታ ወደ ሃገሩ መለሰችው። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ፈተና ገጠመው። አንድ ቀን እመቤታችን በተወለደችበት ግንቦት ፩ ቀን ቅዳሴ "ማን ይቀድስ?" ሲባል ሰዎቹ "አባ ሕርያቆስ ይሁን።" አሉ።
እርሱ ግን "እኔ አይቻለኝም፤ እናንተ ሊቃውንት ቀድሱ።" አላቸው። "አይሆንም" ብለው እርሱኑ አስገቡት። ይህንን ያደረጉት ለተንኮል ነበር። ልክ ወንጌል ተነቦ ፍሬ ቅዳሴ ሲመረጥ እርሱ "እግዚእን (የጌታ ቅዳሴን) ልቀድስ?" ቢል እነርሱ "የሚቀደሰው የሊቅ ቅዳሴ ነው።" አሉት።
ይህንን ያሉት እርሱ የሊቃውንቱን ቅዳሴ አያውቅምና በሰው ፊት እንዲዋረድ ነው። እንዲህም ብለው ባለመማሩ ተሳለቁበት። አባ ሕርያቆስ ግን እያዘነ ወደ መንበሩ ዞረ። ድንግልንም "እመቤቴ መናቄን መገፋቴን ተመልከች።" አላት።
ወዲያው ግን ድንግል ማርያም ወርዳ ቀጸበችው (ጠራችው)። በዘርፋፋው ቀሚሷ ላይም ረቂቅ የሆነ ቅዳሴን አሳየችው። ደጉ ሰው ደስ ብሎት "ጐሥዐ ልብየ" ሲል ሁለቱ እግሮቹ ከመሬት ከፍ አሉ። እርሱም "ወአነ አየድእ ቅዳሴሃ ለማርያም" ብሎ እስከ ኃዳፌ ነፍሱ ድረስ አደረሰው።
ሕዝቡና ካህናቱ በሆነው ነገር ሲደነቁ አንዳንዶቹ "ዝም ብሎ ነው የቀባጠረ።" አሉ። ቅዱሱ ግን ቅዳሴ ማርያምን በብራና ጠርዞ በሕዝቡ መካከል ድውይ ፈወሰበት። እሳት ሳያቃጥለው ውኃ ሳይደመስሰው ቀረ።
መጽሐፈ ቅዳሴው ሙትንም አስነስቷል። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ በዘመኑ ቁጥር አንድ ሊቅ ሆነ። ብዙ መጻሕፍትን ሲተረጉም አጠቃላይ ድርሰቶቹም እልፍ (አሥር ሺህ) ናቸው። ሊቁ እንዲህ በንጹሕ ተመላልሶ ዐርፏል። ይህቺ ቀን ለቅዱሱ የልደቱና ዕረፍቱ መታሰቢያ ናት።
<3 ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ <3
ቅዱስ ሳዊሮስ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው። ወቅቱ መለካውያን (ሁለት ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው። ሊቃውንት "አንበሳ" ሲሉ ይጠሩታል።
ቅዱሱ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ብዙ ሆኖላታል። የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል። ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ።
ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ?" አለችው። እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም።" ሲል መለሰላት። አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት።
እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ። መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው። ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጓዘ። እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ።
በምድረ ግብጽም የጵጵስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ፤ አጸና። በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ።
አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት። ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የካቲት ፲፬ ቀን ዐርፏል። ይህቺ ቀን ዕለተ ስደቱ ናት።
አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት የድንግል እመቤታችንን ጣዕሟን ፍቅሯን ያሳድርብን። የአበውን ሃብትና በረከትም አይንሳን።
<3 አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ <3
አቡነ ገሪማ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሮም ውስጥ ነው። ወላጆቻቸው መስፍንያኖስ እና ሰፍንግያ እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት ነበሩ። ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ።
እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው። ስሙን ይስሐቅ ብለው አሳደጉት። ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ። ለሰባት ዓመታት ሕዝቡን በፍትሕ እያስተዳደረ መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል።
አንድ ቀን ግን ከግብጽ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው። ላኪው አባ ጰንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ ንግሥና ምን ያደርግልሃል? ይልቁኑስ በሰማይ ለዘላለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና!" የሚል ነበር።
ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ። ድንገት ግን ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብጽ አባ ጰንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው።
እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው። ሰውነታቸውን በገድል ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር።
አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው አባ ጰንጠሌዎን አዘኑ። ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ።" አሉ። አባ ይስሐቅ ግን "ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል።" ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (ሁለት መቶ ሜትር) ተጠራርጎ ሸሸ።
ይህንን የተመለከቱት አባ ጰንጠሌዎን "ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)።" አሏቸው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም "አቡነ ገሪማ" ተብለው ቀሩ።
አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም ግሩም ነህ።" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል። ይህም የተደረገው በዚህች ዕለት መስከረም ፴ ቀን ነው።
ጻድቁ ወንጌልንና ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል፦
፩. ስንዴ ጧት ዘርተውት በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር። "በጽባሕ ይዘርዕ ወበሠርክ የአርር" እንዲል።
፪. ጧት የተከሉት ወይን በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር።
፫. አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጠበል ሆኖ ዛሬም አለ።
፬. ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች።
፭. አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን አቁመዋታል።
ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። "ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገ እስከ አሥራ ሁለት ትውልድ እምርልሃለሁ። አንተ ግን ሞትን አትቀምስም።" ብሏቸው ተሰወረ። ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ ብሔረ ሕያዋን አድርሰዋቸዋል።
አምላከ አበው ምሥጢራቸውን አይሰውርብን። ከበረከታቸውም ያድለን።
መስከረም ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፪.አባ ሣሉሲ ክቡር ጻድቅ
፫.ብፁዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
፬.ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስ ሐዋርያት (ለወንጌል የተጠሩበት /ማር. ፩፥፲፱/)
፭.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ
፮.አባ አብሳዲ ዘደብረ ማርያም
፯.አባ አሮን ዘገሊላ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
፪.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ። ሐሴትንም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና።"
(ማቴ ፭፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።
"ሰላም ለአርሴማ ቅድስት ከመ በቀልት ዘይመስል ቆማ
ወዘከለላ ዘመንፈስ ግርማ
ዘፈጸመት ገድላ በጻማ
ወበመንግሥተ ሰማይ ዐቢይ ስማ።"
"ገድሏን በሥቃይ የፈጸመች፤ የመንፈስ ግርማ የጋረዳትና ቁመቷ እንደ ዘንባባ የሚመስል ለምትሆን ለቅድስት አርሴማ ሰላምታ ይገባል፤ በመንግሥተ ሰማይም ስሟ ታላቅ ነው።"
(አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)
መስከረም ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ (ሰማዕታት)
፪.ቅዱስ አንጢላርዮስ ጻድቅ
፫.ቅድስት ጤቅላ ሐዋርያዊት
፬.አባ ዮሐንስ ዘደብረ ጽጌ
ወርኀዊ በዓላት
፩.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪.አቡነ መብዐ ጽዮን ጻድቅ
፫.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፮.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
"ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና። በጐ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና። ስለዚህም 'አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቷል።' ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ። ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቷል።"
(፪ቆሮ ፱፥፩-፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።
እንኳን ለጻድቁ አባታችን አባ አብዱልማዎስ ገዳማዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አባ አብዱልማዎስ ገዳማዊ <3
ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆኑ በበርሃ ሰው ሳያዩ ለሰባ ዓመታት በቅድስና ኑረዋል። በጊዜውም እግዚአብሔር አባ አብዱልማዎስን ወደ አባ ዕብሎይ ልኳቸው ነበር። ሁለቱ ተገናኝተው አብረው ለሦስት ቀናት ሲቆዩ ቅዱስ መልአክ እየተገለጸ አጽናንቷቸዋል። ከሥውራን ማኅበርም ተቀላቅለው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለዋል።
አባ ዕብሎይ ሲያርፍ አንበሶች እያገዟቸው ቀብረዋቸዋል። እርሳቸውም "እኔን የሚቀብረኝ ስጠኝ።" ብለው ጸልየው ነበርና ሦስት ገዳማውያን መጥተውላቸዋል። የካቲት ፭ ቀን አባ ዕብሎይን ገንዘው ቀብረው በሦስተኛው ቀን አርፈዋል።
የአብ በረከት፣ የወልድ ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት፣ የድንግል ማርያም ምልጃ፣ የቅዱሳኑ ጸጋ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን።
የጻድቁ ክብር ይደርብን።
የካቲት ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ አብዱልማዎስ ገዳማዊ
፪.አባ ቴዎድሮስ ሊቀ ጳጳሳት
፫.አባ እለ እስክንድሮስ ሊቀ ጳጳሳት
፬.ቅዱስ አባዲር
ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ
"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ። ሐሴትም አድርጉ።"
(ማቴ ፭፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለአባ ብሶይ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዕብሎይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አባ ብሶይ (ጴጥሮስ) <3
ብሶይ (ቢሾይ) በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተለመደ የቅዱሳን ስም ነው። በተለይ በምድረ ግብጽ በዚህ ስም ሰማዕታትም ጻድቃንም ተጠርተውበታል። ከእነዚህ ቅዱሳን (ከገዳማውያኑ) አንዱ የሆነው አባ ብሶይም (አንዳንዴ አባ ጴጥሮስም ይባላል።) የዘመነ ጻድቃን ፍሬ ነው።
ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ቤት ናት። ያ ማለት ራሳቸውን ለክርስቶስ የለዩ ሰዎች ይኖሩባታል። እነዚህ ሰዎች ከተለያየ ጐዳና እና ማንነት ሊመጡ ይችላሉ። ቢያንስ ግን በንስሐ የታጠቡ መሆናቸው ወደ ተቀደሰው አንድነት እንዲገቡ ትልቅ መሠረት ይሆናቸዋል።
ቅዱሳንም አንዳንዶቹ ከእናታቸው ማኅጸን ሲመረጡ ሌሎቹ ደግሞ ከኃጢአት ሕይወት የተመለሱ ሆነው ይታያሉ። ደስ የሚለው ደግሞ በንስሐ ከታጠቡ በኋላ በፍጹም ልባቸው በመጋደላቸው እነሆ በሰማያዊ አክሊል ተከልለዋል።
አባ ብሶይ ጴጥሮስም ከኃጢአት ተመልሰው ለቅድስና ከበቁ ቀደምት አበው አንዱ ነው። ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ምድረ ግብጽ የታወቀ ሽፍታ፣ ዝሙተኛና ክፋቱ የተገለጠ ሰው ነበር። ለብዙ ዘመናት በእንዲህ ካለ ግብሩ መላቀቅ ባይችል እግዚአብሔር ጥሪውን ላከለት።
የአምላካችን የጥሪ መንገዱ ብዙ ነውና ለእርሱ ደዌን ላከለት። መቼም ወደድንም ጠላንም በሽታ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ጥሩ ፈሊጥ (አጋጣሚ) ነው። ዛሬም ቢሆን ዘለን ዘለን ስንሰበርና የሐኪም መፍትሔ ሲጠፋ የግዳችን ወደ እግዚአብሔር ቤት (ወደ ጠበሉ) እንቀርባለንና። አምላካችን ስለዚህ ጥበቡ ይክበር ይመስገን።
ቅዱስ አባት ብሶይም በሽፍትነትና በኃጢአት ኑሮ ሳለ ለሞት የሚያበቃ ደዌ ደርሶበት የአልጋ ቁራኛ ሆነ፤ ኃይሉም ደከመ። በእንዲህ እያለም በራእዩ ያየው ነገር ፍጹም አስደነገጠው። መላእክት ነፍሱን ወስደው መካነ ኩነኔን ካሳዩት በኋላ አለቀሰ።
ይልቁን ሌቦችና ዝሙተኞችን ከአራት ሲቆራርጣቸው ስላየ ፈጽሞ አዘነ፤ ተጸጸተ። ፈጣሪውንም ዕድሜ ለንስሐ እንዲሰጠው ተማጸነ። ጌታንም "አምላኬ ሆይ! ከበሽታዬ ብታድነኝ ዳግመኛ አልበድልህም። ዓለምን ሁሉም ንቄ አገለግልሃለሁ።" ሲል ተማጸነው።
እግዚአብሔርም ሰምቶት ፈጥኖ ፈወሰው። አባ ብሶይም እንደ ቃሉ በፍጹም ልቡ ንስሐ ገብቶ መነነ። በገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ሲኖር የላመ የጣመ በልቶ ከሞቀ መኝታ ተኝቶ አያውቅም።
ሰውነቱን ይቀጣት ዘንድም እስከ ሠላሳ ቀን ያለ እህል ውኃ ይጾም ነበር። በዘመኑ ሁሉም የሴት መልክን አላየም። ንስሐን የሚወድ ጌታም ጸጋውን አብዝቶለት ብዙ ድርሳናትን ጽፏል። የሚገርመው ደግሞ ከትህትናውና ቅድስናው የተነሳ የእያንዳንዱ ሰው ኃጢአት ተገልጦ ይታየው ነበር።
ቅዱሱ አባታችን ብሶይ ጴጥሮስ በንስሐና በቅድስና ሕይወት እንዲህ ተመላልሶ በዚህች ቀን ዐርፎ በገዳሙ ተቀብሯል። የድካሙን ዋጋም አድልዎ ከሌለበት ከእውነተኛው ፈራጅ ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብሏል።
<3 ቅዱስ ዕብሎይ <3
አባ ዕብሎይ በቀደመ ሕይወቱ ለአርባ ዓመታት በኃጢአት የኖረ፣ እግዚአብሔር ለንስሐ ሲጠራው "እሺ" ብሎ ለአርባ ዓመታት በንስሐ ሕይወት ተመላልሶ በበርሃ የተጋደለ፣ እንባው እንደጐርፍ ይፈስ የነበረ፣ አጋንንትንም ድል የነሳና ለፍሬ ለትሩፋት የበቃ ቅዱስ አባት ነው። እግዚአብሔርም ብዙ ቃል ኪዳን ገብቶለታል።
"ባርያ ሆኖ ያለ ኃጢአት ጌታ ሆኖ ያለ ምሕረት የለምና ይቅር በለን!"
(የአባ ዕብሎይ የንስሐ ጸሎት)
አምላከ ቅዱሳን ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ አይንሳን። ከክብረ ቅዱሳንም ያካፍለን።
አምላክ በበረከታቸው ይባርከን።
የካቲት ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ብሶይ ጻድቅ
፪.ቅዱስ አባ ዕብሎይ ገዳማዊ
፫.አባ አክርጵዮስ
፬.አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት (ፍልሠታቸው)
፭.ቅዱስ አሞኒና ሚስቱ ቅድስት ሙስያ (የታላቁ ዕብሎይ ወላጆች)
፮.አባ ኖብ ጻድቅ መነሳንሱ ዘወርቅ
፯.ቅዱሳን አባ አሞኒና አባ ዮሐኒ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
፫.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፭.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል። ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ።' ይላቸዋል። እላችኋለሁ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።"
(ሉቃ ፲፭፥፬-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለማሪ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እና ለአበው አባ ያዕቆብ ወአባ ዕብሎይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ <3
እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ፪፻፺፰ (፫፻፮) ዓ.ም ነው። ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ። (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም።)
ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር። የሰማዕትነት፣ የሐዋርያነት፣ የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው። ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ።
ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምህርት ነው። የሚገርመው መምህሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይህንኑ አጥብቆ አስተምሮታል።
ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር። ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና። እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት ይገዛላትም ገባ።
በጊዜው እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር። እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን (ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት፣ ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር።
በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ፫፻፲፰ (፫፻፳፭) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምህረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምህርትና በረከትን አግኝቷል።
ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራእይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይህማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው።" አለው። እርሱም መምህሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ። ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል።
በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል። ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር። ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር። "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ እንደ እንጀራ ተመግቤው እንደ ውኃ ጠጥቼው እንደ ልብስም ተጐናጽፌው።" እያለ ይመኝ ነበር።
አፍጣኒተ ረድኤት ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት። ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት። ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ በፊቱ ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ በፊቷ ቆሞ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ነው።
ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች። ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል። ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው።
እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ - የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ።" ብሎ ጸልዩዋል። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ "ተክሪት" በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል።
በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል። የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል። ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል። በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል፤ ተአምራትንም ሠርቷል። በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ፫፻፷፭ (፫፻፸፫) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል።
ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል።
ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን፦
፩.ቅዱስ ኤፍሬም
፪.ማሪ ኤፍሬም
፫.አፈ በረከት ኤፍሬም
፬.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም
፭.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም
፮.አበ ምዕመናን ኤፍሬም
፯.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም አባታችን አንተ ነህ!
ዛሬ ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዓመታዊ የፍልሠት በዓሉ ነው።
ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን፣ ክብሩን፣ አእምሮውን፣ ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን፤ አሳድሪብን። አሜን!
<3 አባ ያዕቆብ ገዳማዊ <3
ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት "ለስሒት መኑ ይሌብዋ - ስሕተትን ማን ያስተውላታል።" (መዝ. ፲፰፥፲፪) ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ታላቅ ቅዱስ ሰው በኃጢአት ብዙ ተፈተነ። ወደ በርሃ ወጥቶ በምናኔ ጸንቶ በጾምና በጸሎት ተግቶ ዘመናትን ስላሳለፈ ሰይጣንን አሳፈረው።
ግን ደግሞ ክፉ ጠላት ባልጠረጠረው መንገድ መጥቶ መከራ ውስጥ ከተተው። የአገረ ገዢው ልጅ ታማ "ፈውሳት" አሉት፤ እርሱም ፈወሳት። ወደ ቤቷ ስትመለስ ግን አመማት። "ከአንተ ጋር ትቆይ።" ብለው ትተዋት ቢሔዱ ከመለማመድ የተነሳ በዝሙት ወደቀ።
እንዳይገለጥበት ስለ ፈራም ገደላት። በሆነው ነገር ተስፋ ቆርጦ ወደ ዓለም ሲመለስ ቸር ፈጣሪ የሚናዝዝ አባትን ልኮ ንስሐ ሰጠው። ጉድጓድ ምሶ ድንጋይ ተንተርሶ ለሠላሳ ዓመታት አለቀሰ። እግዚአብሔርም ምሮት የቀደመ ጸጋውን ቢመልስለት ዝናምን አዝንሞ ሕዝቡን ከእልቂት ታድጓል። በዚህች ዕለት ዐርፎም ለርስቱ በቅቷል።
<3 ታላቁ አባ ዕብሎይ <3
ይህ ቅዱስ የአቡነ አቢብ ደቀ መዝሙር ሲሆን በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳንም ቀዳሚው ነው። ብዙ መጻሕፍት "ርዕሰ ገዳማውያን" ይሉታል። የቅዱሱ ተጋድሎ እጅግ ሰፊ ነው።
የአባቶቻችን በረከት ይደርብን።
የካቲት ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፪.አባ ያዕቆብ መስተጋድል
፫.ቅዱስ አባ ዕብሎይ ገዳማዊ (ሕይወቱ መላእክትን የመሰለ ግብጻዊ አባት)
ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም
፪.ቅዱስ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት
፫.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፬.ቅዱሳን ዘካርያስ ወስምዖን
፭.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፮.አባ ዜና ማርቆስ ጻድቅ
፯.አባ መድኃኒነ እግዚእ (ዘደብረ በንኮል)
"ለምኑ ይሰጣችሁማል። ፈልጉ ታገኙማላችሁ። መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና። የሚፈልገውም ያገኛል። መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል።"
(ማቴ ፯፥፯-፰)
"የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፴-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ገዳማዊ አባ ጳውሊ እና ለጻድቁ አባ ለንጊኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ታላቁ ቅዱስ ጳውሊ <3
በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ /ዐቢይ/ THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው። አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን።
ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው። በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል። ሕይወቱ በጐላ በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው።
ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል።
ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለአርባ ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል፤ አስተምሯል። በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት።
ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። አኗኗራቸውም በቡድንም በነጠላም ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው። ይህም ሲያያዝ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደረሰ። በዚህ ዘመን ግን አባ ጳውሊ የሚባል ንጹሕ ክርስቲያን ይህንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው። ለሰማንያ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ። ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ።
ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት። በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ። ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ።
እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል። ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል።
አንድ ቀን ቅዱስ እንጦንስ (የመነኮሳት ሁሉ አባት) እንዲህ ሲል አሰበ። "በውኑ በበርሃ ለበርካታ ዘመናት በመኖር ከእኔ የሚቀድም (የሚበልጥ) ሰው ይኖር ይሆን?"
ይህንን ሃሳቡን ገና ሳይጨርሰው ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ ዘንድ ደረሰ።
"እንጦንስ ሆይ! ከእኔ የሚቀድም የበርሃ ሰው ይኖር ይሆን ብለህ አስበሃል። በእርግጥም ከአንተ ሃያ ዓመታትን ቀድሞ ወደ በርሃ የገባ፣ በቅድስናው ፈጣሪውን ያስደሰተ፣ ዓለም ከነ ክብሯ የእግሩን መረገጫ ያህል እንኳ የማትመጥነው በጸሎቱና በምልጇው ዓለም የምትጠበቅለት ሞገስን የተሞላ አንድ ሰው በበርሃ ስላለ ሒድና ተመልከተው።" ብሎት ተሠወረው።
ቅዱስ እንጦንስም ከሰማው ነገር የተነሳ እየተደነቀ ተነሳ። እርሱ ካለበት በርሃ በራቀ መንገድም ለቀናት ተጉዞ አንድ በዓት (ዋሻ) በር ላይ ደረሰ። በበሩ አካባቢ የሰውና የአራዊት ኮቴ ተመልክቶ በሩን ጸፋ (ቆፈቆፈ)። በውስጥ ያለው አረጋዊ ሰው ግን ትልቅ ድንጋይ ገልብጦ በሩን አጠበቀው። ለሰማንያ ዓመታት ሰውን አይቶ አያውቅምና ሰይጣን ሊያታልለኝ መጥቷል ብሎ አስቧል። ቅዱስ እንጦንስ ግን "ኃሠሥኩ እርከብ ጐድጐድኩ ይትረኃው ሊተ - ሽቻለሁና ላግኝ፤ ደጅ መትቻለሁና ይከፈትልኝ።" ሲል አሰምቶ ተናገረ።
ቅዱሱ ገዳማዊም ሰው መሆኑን ሲያውቅ በሩን ከፈተለትና ወደ ዋሻው አስገባው። መንፈሳዊ ሰላምታንም ተለዋወጡ። ሲመሽም ቅዱስ እንጦንስ ሽማግሌውን ገዳማዊ "ስምህ ማን ነው?" ቢለው "ስሜን ካላወክ ለምን መጣህ?" ሲል መለሰለት።
ያን ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ቀና ብሎ ሰማይን ሲመለከት ምሥጢር ተገለጠለትና "ቅዱስ ጳውሊ ሆይ! ከአንተ ጋር ያገናኘኝ ፈጣሪ ይክበር፤ ይመስገን።" ሲል ፈጣሪውን ባረከ። ቅዱስ ጳውሊም መልሶ (በጸጋ አውቆት) "አባ እንጦንስ ሆይ! እንኳን ደህና መጣህ።" አለው። ሁለቱም ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ተጨዋወቱ።
ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ዓይነት የቅድስና ሕይወት የመጀመሪያ የምትላቸው አላት። ለምሳሌ፦
የመጀመሪያው ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስ፣
የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ፣
የመጀመሪያው ባሕታዊ (ገዳማዊ) ቅዱስ ጳውሊ እና የመጀመሪያው መነኮስ ቅዱስ እንጦንስን ማንሳት እንችላለን።
ቅዱስ ጳውሊ የተወለደው በሰሜናዊ ግብጽ በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው። ወላጆቹ ባለጸጐች ነበሩ። ቅዱሱንና ታላቅ ወንድሙን አባ ጴጥሮስን ወልደዋል። ሁለቱ ክርስቲያን ወንድማማቾች ገና ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው። ሃዘናቸውን ፈጽመው ሃብት ሲካፈሉ ግን መስማማት አልቻሉም።
ምክንያቱ ደግሞ ትልቁ ጴጥሮስ ደህና ደህናውን እቃ ወስዶ መናኛ መናኛውን ለትንሹ ለጳውሎስ (ጳውሊ) መስጠቱ ነበር። ስለዚህ ነገር ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሔዱ ግን መንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሙቶ ደረሱ።
ቆመው ሳሉም ቅዱስ መልአክ ሰው መስሎ ጳውሊን "ይህ ሰው ባለጸጋ ነው። በገንዘቡ የሰጠውን ፈጣሪ ሲበድልበት ኑሮ እነሆ ተሸኘ። በሰማይም አስጨናቂ ፍርድ ይጠብቀዋል።" ሲል ነገረው።
በዚያች ቅጽበት የወጣቱ ጳውሊ ሐሳብ ተለወጠ። ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ! ሁሉ ንብረት ያንተ ይሁን።" ብሎት ከአካባቢው ጠፋ። በመቃብር ሥፍራ ለሦስት ቀናት ያለ ምግብ ጸልዮ የእግዚአብሔር መልአክ ሰው ወደ ማይደርስበት በርሃ ወሰደው።
በዚያም ምንጭ ፈለቀችለት። እየጾመ ይጸልይ ይሰግድ ገባ። ሁሌ ማታ ግማሽ ሕብስት ከሰማይ እየወረደለት ቅዳሜና እሑድ መላእክት እያቆረቡት ለሰማንያ ዓመታት ኖረ። (አንዳንድ ምንጮች ግን ለዘጠና ዓመታት ይላሉ።) ከቅዱስ እንጦንስ ጋር የተገናኙትም ከዚህ በኋላ ነው።
ከቅዱስ እንጦንስ ጋር በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታም ቅዱስ ጳውሊ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል። በዚህች ቀን ሲያርፍም መቃብሩን አናብስቱ ቆፍረዋል። ቅዱስ እንጦንስም በክብር ቀብሮታል። ለሰማንያ ዓመታት የለበሳት የዘንባባ ልብሱም ሙት አስነስታለች።
ጻድቅ፣ ቡሩክ፣ ቀዳሚው ገዳማዊ፣ መላእክትን የመሰለና የባሕታውያን ሁሉ አባት ለተባለ ለቅዱስ ጳውሊ ክብር ይገባል!
<3 አባ ለንጊኖስ <3
ጻድቁ ከኪልቅያ እስከ ሶርያ ከሶርያ እስከ ግብጽ ድረስ በተጋድሎ የተጓዙ አባት ናቸው። በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽም የደብረ ዝጋግ (ግብጽ፤ እስክንድርያ) አበ ምኔት ሆነው አገልግለዋል።
ሙታንን አስነስተው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። ከድንቅ ነገራቸው ሰይጣን የእርሳቸውን የምንኩስና ቆብ ዐይቶ ደንግጦ መሸሹን እንጠቅሳለን።
"ኀበ ኢኀሎከ ሶበ ቆብዓከ ርዕየ
ሰይጣን ተኃፊሮ እፎኑመ ጐየ።" እንዲል።
(አርኬ)
አምላክ በበረከታቸው ይባርከን።
እንኳን ለቅዱሳት አንስት ሶፍያ ወአዋልዲሃ፣ ኦርኒ ወማኅበራኒሃ እና ለሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅድስት ሶፍያና ልጆቿ <3
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታዋቂ ከሆኑ የእናቶቻችን ስሞች "ሶፍያ" ቀዳሚው ነው። ቃሉ በጥሬው ሲተረጐም "ጥበብ (ጥበበ ክርስቶስ) Wisdom of God" ማለት ነው። ከጻድቃንና ከሰማዕታት ወገን በዚህ ስም የተጠሩ እናቶች አሉ።
ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው በዕለቱ የምናስባት እናት ቁጥሯ ከሰማዕታት ነው። ዋናው ዘመነ ሰማዕታት ከመጀመሩ በፊት የነበረችው ቅድስት ሶፍያ ከሕግ ትዳር ሦስት ሴቶች ልጆችን አፍርታለች።
ስማቸውንም ጲስጢስ (ሃይማኖት)፣ አላጲስ (ተስፋ) እና አጋጲስ (ፍቅር) ስትል ሰይማቸዋለች። እንደሚገባም በሥርዓቱ አሳድጋ እድሜአቸው ዘጠኝ፣ አሥር እና አሥራ ሁለት ሲደርስ ለሰማያዊ ሙሽርነት አጭታቸዋለች።
በዘመኑ "ክርስቶስን ካዱ።" የሚል መሪ ተነስቶ ነበርና ቅዱሳቱ በመድኃኒታችን አምነው ጣዖትን ዘልፈው አንገታቸውን ሰጥተዋል። ክብረ ሰማዕትን ሃገረ ክርስቶስንም ወርሰዋል።
<3 ቅድስት ኦርኒ ሰማዕት <3
"ኦርኒ" ማለት በምሥራቃውያን ልሳን "ሰላም" ማለት ነው። ቅድስቲቱ አርበኛ የዘመነ ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን ፍሬ ስትሆን ተወልዳ ያደገችውም በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ነው።
ምንም ዛሬ ያለ ትውልድ ቢዘነጋት ቅድስት ኦርኒ ተወዳዳሪ የሌላት ሰማዕት፣ ሐዋርያዊት፣ ድንግል ናት። እርሷ ውበቷን፣ ንግሥናዋን፣ ክብሯን፣ ሃብቷን፣ ወጣትነቷንና ያላትን ሁሉ ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ሰውታለችና ክብርት ናት።
በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ቤተ መንግሥት የተወለደችው ቅድስት ኦርኒ እስከ ወጣትነቷ ድረስ ክርስቶስን ልታውቀው አልተቻላትም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ንጉሡ አባቷ ጣዖትን ማምለኩ ነበር።
ንግሥት እናቷ ምንም ክርስቲያን ብትሆንም ስለ ክርስትና ልትነግራት አልደፈረችም። ይህን ብታደርግ የሚደርስባትን መከራ ታውቃለችና። ግን ደግሞ ውስጥ ውስጡን ትጸልይላት ነበርና ፈጣሪ መንገዱን ሊከፍት ጀመረ።
መምለኬ ጣዖት አባቷ ሰው እንዳያያት ቤተ መንግሥት ሠርቶ፣ አሥራ ሁለት ሞግዚቶችን መድቦ ጣዖት ከፊቷ አቁሞ ለዘመናት ዘጋት። የሚገርመው ግን መልኳን እንዳያይ በበር ሆኖ የሚያስተምራት ፈላስፋ ተቀጥሮ ነበርና የዚህ ሰው ማንነቱ ነው።
መምለኬ ክርስቶስ ደግ ሰው ነበርና ፈሊጥን ይሻላት ገባ። በዚህ መካከል ቅድስት ኦርኒ ራእይን ታያለች። የቤቷ መስኮቶች ተከፍተው ሳሉ በስተምሥራቅ ነጭ ርግብ የዘይት (የወይራ) ዝንጣፊ ይዛ ገብታ ከማዕዷ ላይ ጥላው ወጣች።
እርሷን ተከትሎ ቁራ በምዕራብ ገባ። እባቡን ማዕዷ ላይ ጣለው። በሦስተኛው ደግሞ ንስር ገብቶ አክሊል ትቶላት ወጣ። ቅድስቲቱም እየገረማት አረጋዊ መምህሯን "ተርጉምልኝ" አለችው።
እርሱም፦
"ርግብ = ጥበብ (መንፈስ ቅዱስ)፣
ዘይት = ጥምቀት፣
ቁራ = ክፉ ንጉሥ፣
እባብ = መከራ፣
ንስር = ድል ነሺነት (ልዑላዊነት)፣
አክሊልም = ክብረ ሰማዕታት ነው።" ብሎ ተርጉሞ ክርስቲያን ሆና ይህ ሁሉ እንደሚደረግ ነግሮ ተሰናበታት።
እርሷም ስትጸልይ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አጽናናት። ያጠምቃትና ያስተምራት ዘንድም ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስን ልኮላታል። ሐዋርያውም የቤተ መንግሥቱን ግድግዳ ሰንጥቆ ገብቶ ለሰማያዊ ሙሽርነት የሚያበቃ ትምህርትና ጥምቀትን ሰጥቷት ሔዷል።
ቅድስት ኦርኒም የአባቷን ጣዖታት ቀጥቅጣ ሰብራ ከአባቷ ጋር ተጣላች። እርሱም "እገድላታለሁ" ብሎ በእንስሳት ጅራት ላይ ጸጉሯን ሲያስር እንስሶቹ ደንብረው እጁን ገንጥለው መሬት ላይ ጥለው ገደሉት። ቅድስት ኦርኒ ግን ጸሎት አድርሳ አባቷን ከሞት አስነሳችው፤ እጁንም ቀጠለችለት።
በዚህ ምክንያት በዚያች ዕለት ብቻ አባቷና ሠላሳ ሺህ የከተማው አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል። ቅድስት ኦርኒ ግን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ታጥቃ ክርስትናን ሰበከች፤ ብዙም ተሰቃየች። ንጉሡ ዳኬዎስ፣ ልጁና ሌሎች ሁለት ያህል ነገሥታት በእሳት፣ በአራዊት፣ በግርፋትና በጦር ፈትነዋታል።
እርሷ ግን ሁሉን በኃይለ ክርስቶስ ድል ነስታለች። ሙታም የተነሳችበት ጊዜ አለ። በመጨረሻም በዚህች ቀን ወደ ሰማያዊ ርስት (ገነት) ተመስጣለች። በዘመነ ስብከቷ ካሳመነቻቸው ባሻገር አሥራ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ለሰማዕትነት እንዲበቁም ምክንያት ሆናለች።
<3 ቅዱስ ጐርጐርዮስ ታኦሎጐስ <3
ቅዱሱ፦
የዘመነ ሊቃውንት ፍሬ፣
የእንዚናዙ ኤጲስ ቆጶስ፣
የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ፣
የጉባዔ ቁስጥንጥንያ (በ፫፻፹፩ ዓ.ም) ሦስተኛ ሊቀ መንበር፣
ባለ ብዙ ድርሳን፣
የቂሣርያ (ቀጰዶቅያ) ኮከብ፣
ብሩህ ገዳማዊና መልካም እረኛ የነበረ አባት ነው።
መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በጻፋቸው ብዙ መጻሕፍትና በስብከቱ ከሊቃውንት ወገን "ታኦ(ዎ)ሎጐስ" ተብሎ የተጠራ እርሱ ብቻ ነው። ትርጉሙም በግዕዙ "ነባቤ መለኮት" ማለት ነው። በአማርኛም "አንድነትን ሦስትነትን የተናገረ (ያመሠጠረ)" እንደ ማለት ነው። ቅዱሱ ዛሬ ዕረፍቱ ነው።
አምላከ ቅዱሳን ከበረከታቸው ይክፈለን።
በመጽናታቸውም ያጽናን።
እንዲህ ኃጢአታችን ጽዋዑን ሞልቶ በተረፈበት በዚህ ዘመን አንዲት ሰዓትም ውድ የሆነች የንስሐ ዕድሜ ናት። እግዚአብሔር ግን ደግ ነውና ይሔው ጥርን አስፈጸመን። ባይገባን ነው እንጂ በዚህች ወር ውስጥ ሚሊየኖች በደዌ የአልጋ ቁራኛ ሁነዋል።
ሚሊየኖችም ለንስሐ ሳይበቁ እንዲሁ አንቀላፍተዋል (ሙተዋል)። እስኪ እርሱ አምላካችን ቀሪውን ዘመን ደግሞ ለንስሐና ለመልካም ሥራ ባርኮ ይስጠን።
ወርኀ ጥርን በቸር ያስፈፀመ አምላከ ቅዱሳን ወርኀ የካቲትን እንዲባርክልን እንለምነው።
ጥር ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ሶፍያና ሦስቱ ሰማዕታት ልጆቿ (ጲስጢስ፣ አላጲስና አጋጲስ)
፪.ቅድስት ኦርኒ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬.አባ አክርስጥሮስ
፭.አምስቱ ደናግል ሰማዕታት (ጤቅላ፣ ማርያ፣ ማርታ፣ አበያና ዓመታ)
፮.ጻድቃነ ዴጌ (የተሠወሩበት)
፯.አባ ሚናስ ሊቀ ጳጳሳት
፰.አሥራ ሦስት ሺህ ሰማዕታት (የቅድስት ኦርኒ ማኅበር)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ
፪.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፫.አባ ሣሉሲ ክቡር
"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።"
(፩ጴጥ ፫፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለጌታችን አማኑኤል ክርስቶስ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ተአምራተ እግዚእ <3
"ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል። መሠረታዊ መልእክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው። ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ) ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል።
ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው። ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ - ከሐሌ ኩሉ - ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው።
እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል። በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ፣ መና ሲያዘንሙ፣ ውኃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት።) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ፣ እሳትን ሲያዘንሙ፣ ሙታንን ሲያስነሱ (፩ ነገሥት) እንደ ነበር ይታወቃል።
እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል። በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል።
(ማቴ. ፲፥፰ ፤ ፲፯፥፳ ፣ ማር. ፲፮፥፲፯ ፣ ሉቃ. ፲፥፲፯ ፣ ዮሐ. ፲፬፥፲፪)
እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል።
(ሐዋ. ፫፥፮ ፤ ፭፥፩ ፤ ፭፥፲፪ ፤ ፰፥፮ ፤ ፱፥፴፫-፵፫ ፣ ፲፬፥፰ ፤ ፲፱፥፲፩)
ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል። እያንዳንዱ ግን ቢጻፍ ዓለም ለራሷ ባልበቃች ነበር። ከእነዚህ መካከልም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በዚህች ዕለት በሰባት እንጀራ እና በጥቂት ዓሣ ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨምር አራት ሺህ ሰዎችን በቸርነቱ አበርክቶ አጥግቧል። ደቀ መዛሙርቱም ሰባት ቅርጫት ማዕድ አንስተዋል።
ጌታችን በከሃሊነቱ የተራቡትን ሲያጠግብ እንዲሁ አይደለም። በጊዜው የነበሩ አይሁድ ጠማሞች ነበሩና እነርሱን ምላሽ በሚያሳጣ መንገድ ነበር እንጂ። አይሁድ ላለማመን ብዙ ጥረት ነበራቸውና።
በዚህች ዕለትም እንጀራውን አበርክቶ ሲያበላቸው፦
፩.ጊዜው አመሻሽ ላይ ነበር። ምክንያቱም ጧት ላይ ቢሆን ከቤታችን የበላነው ሳይጐድል ብለው ከማመን ይርቁ ነበርና።
፪.ከውኃ ዳር አድርጐታል። መታጠቢያ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ።
፫.ሳር የበዛበት ቦታ ላይ አድርጐታ። ምክንያቱም መቀመጫ ብናጣ በደንብ ሳንበላ ቀረን እንዳይሉ።
፬.ከከተማ አርቆ ምድረ በዳ ላይ አድርጐታል። ያማ ባይሆን "ፈጣን ፈጣን ደቀ መዛሙርቱ ተሯሩጠው እየገዙ አቀረቡለት።" ባሉ ነበርና።
ለመድኃኒታችን ክርስቶስ አምልኮና ምስጋና ይሁን!
አማኑኤል አምላካችን ጣዕመ ፍቅሩን ያሳድርብን።
ጥር ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሰማዕት (ስለ ሃይማኖት ሰባት ጊዜ ሙቶ የተነሳ፣ ሰባት አክሊል የወረደለት)
፪.ቅዱስ አካውህ መነኮስ
፫.ስምንት መቶ ሰማዕታት
፬.ቅዱስ ዮሴፍ አይሁዳዊ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፭.ቅድስት ሳቤላ
ወርኀዊ በዓላት
፩.አባቶቻችን አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ
፪.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
"ጌታ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ 'ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስከ አሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ። በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም።' አላቸው።
ደቀ መዛሙርቱም 'ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?' አሉት። ጌታ ኢየሱስም 'ስንት እንጀራ አላችሁ?' አላቸው። እነርሱም 'ሰባት ጥቂትም ትንሽ ዓሣ' አሉት።
ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ። ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በሉና ጠገቡ። የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሱ። የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ።"
(ማቴ ፲፭፥፴፪-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱሳን አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አረጋውያን ሰማዕታት <3
ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው። ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል። ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው።
ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል። የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው። "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው።
እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ። ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም።
እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ። የሚረግሟችሁን መርቁ። ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ።" ብሎናልና።
(ማቴ. ፭፥፵፬)
ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚሆንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል።
በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል። የቀደሙ ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና።
የእነዚህ ሰማዕታት ቁጥራቸው አርባ ዘጠኝ ሲሆን አባ ቢስዱራ የሚባል ጻድቅ ሰው ሃምሳኛ ሁኖ ይመራቸው ነበር። መኖሪያቸው ገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) ሆኖ ዘመኑ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበር።
ሃምሳውም ሙሉ ዘመናቸውን በምናኔና በቅድስና ፈጽመው በስተእርጅና ደግሞ ሰማዕትነት መጣላቸው። በ፬፻፴ዎቹ ዓ.ም አካባቢ የዚያን ጊዜ በርበር ይባሉ የነበሩት አረማውያኑ (የዛሬዎቹ አሕዛብ አባቶች) "ሃይማኖት ካዱ።" እያሉ ሰይፍን መዘዙባቸው።
በጊዜው አባ ቢስዱራ በማረፉ ኃላፊነቱን የወሰዱት አባ ዮሐንስ ከአርባ ስምንቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ተስማምተው በበርበር እጅ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። ከንጉሥ ቴዎዶስዮስ (ትንሹ) ተልኮ የነበረ አንድ ክርስቲያንም በፍቅረ ክርስቶስ ተስቦ ከወጣት ልጁ ጋር ተሰይፏል። የብርሃን አክሊልም ለሃምሳ አንዱም ወርዷል።
አምላከ ቅዱሳን ከተከፈተ ገነት፣ ከተነጠፈ ዕረፍት በቸርነቱ ያድርሰን።
ጥር ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አርባ ዘጠኝ አረጋውያን ሰማዕታት (ግብጽ ገዳመ አስቄጥስ ውስጥ)
፪.ቅድስት አንስጣስያ (በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከቁስጥንጥንያ ወደ ግብጽ ወርዳ ንግሥናን ንቃ በበርሃ ስትጋደል የኖረች ቅድስት
እናት ናት።)
፫.ቅዱስ ዮሴፍ (መፍቀሬ ነዳያን)
፬.አባ ጽሕማ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ኢትዮጵያዊ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ
ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን።' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ ፰፥፴፭-፴፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር) ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ መርቆሬዎስ ኃያል <3
ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት። ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው።
ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት "ካልዕ (ሁለተኛው) ሊቀ ሰማዕታት" ሲሉ ይገልጹታል።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር "አሮስ" የሚሉት ሰው ይኖር ነበር። ሚስቱ ደም ግባት የሠመረላት እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር።
አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ። እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ። የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል "እንስሳ ተያዘልን።" ብለው ሲሯሯጡ ዓይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው። ሁለት ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ውስጥ ተይዘው ነበር።
እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው። ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል። ግን እጅግ ግዙፍ፣ ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ፣ ወገባቸው እንደ ሰው፣ ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት የሚመስል ነው።
እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም። አንበሳና ነብርን እንኳ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል። ዓይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም። ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ። ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት። አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው።
"ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት።" አላቸው። ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው። በዚህ ጊዜ ሁለቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት። አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶ ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት።
ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች። ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት። ትርጉሙም "መፍቀሬ አብ - የአብ ወዳጅ" ማለት ነው። ከዚያም አሮስ ሚስቱን፣ ልጁንና ሁለቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ ተጠመቀ።
አበው ካህናት እሱን "ኖኅ"፣ ሚስቱን "ታቦት"፣ ልጁን ደግሞ "መርቆሬዎስ" ሲሉ ሰየሟቸው። መርቆሬዎስ ማለትም "ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ - የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው።
ከዚያም ደስ እያላቸው፣ ክርስቶስን እያመለኩ፣ ነዳያንን እያሰቡ፣ ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ። ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ "ካላመጣሃቸው" አለው። ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ።
ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው። በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር። አንድ ጊዜ ግን ሁለቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው። ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል "እንቢ" በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ።
በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ። ንጉሡ ደግሞ ታቦትን "ላግባሽ" ስላላት የአምስት ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች። በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው።
እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር። በኋላ ግን በሕፃኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው። በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው። በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ።
በዚያም ቤተ ክርስቲያንን አንጾ፣ ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጐ ኖኅ ለዓመታት ኖረ። ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ። እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት።
በጦርነት እጅግ ኃያል በሰው ዘንድ ፍጹም ተወዳጅ የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ። ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምዕመናን ላይ ሞት ታወጀ። በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግሥት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸው ዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ።
ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ። ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው።
በማግስቱም "ምን ይሻላል?" ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ "እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻየን እቋቋማቸዋለሁ።" ቢል ሳቁበት።
እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው።) ተጭኖ በርበሮችን "ጠብ ይቅርባችሁ፤ በሰላም ሒዱ።" ቢላቸው ተሳለቁበት። ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ። ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኳ የተረፈ አልነበረም።
ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ። ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ "ድሉ የጣዖቶቼ የነ አጵሎን ነው።" በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ።
በሦስተኛው ቀንም "ለጣዖት ሠዋ።" የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ። ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ። የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው።
"ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ - ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ ለጥፋት ይሁንህ።" ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው። ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው።
ያም አልበቃ ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው።
ለዚያ ነው ሊቃውንት፦
"አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም።" ያሉት።
ከዚያም ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት። ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ፣ በግርፋት፣ በእሳት፣ በስለትም አሰቃየው። በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው። በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር ፳፭ ቀን አንገቱን ሰይፈውታል።
እርሱ ካረፈ በኋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኳል። አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል። ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ፪፻ ዓ/ም እንደ ተወለደ በ፪፻፳ ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ፪፻፳፭ ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል።
ሰማዕቱ በዚህች ዕለት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖችን ያሰቃይና ይገድል የነበረውን ዑልያኖስን ያጠፋበት መታሠቢያ ይከበራል።
የቅዱሱ ክብር ታላቅ ነው።
አምላከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በከበረ ቃል ኪዳኑ ይጠብቀን። ከርስቱም አያናውጠን። ከበረከቱም ይክፈለን።
ቸሩ እግዚአብሔር እድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍሥሃ አይንሳን።
"አባቴ ጊዮርጊስ ሆይ! የልቤን ኀዘን ስነግርህ ፈጥነህ ጸሎቴን ስማኝ፤ ነገሬንም አድምጠኝ።
ያዘኑትን የምታረጋጋ ሆይ ወደ እኔ ቅረብ፤ በአጠገቤም ተገኝተህ አለሁልህ በለኝ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
እንኳን ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ እና ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ <3
ይህ ቅዱስ ሐዋርያ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን መብራት ነው። ወደ ክርስትና የመጣው በ፵ዎቹ ዓ.ም አካባቢ ሲሆን አሳምኖ ለቅድስና ያበቃው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው።
በጊዜውም በነበረው ትጋትና ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል። ሆዱንም እጅግ ያመው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ሲጠራው "የምወድህ ልጄ" እያለ ነበር። በኤፌሶንም ጵጵስናን ሹሞ ሁለት መልእክታትን ልኮለታል። ቅዱስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት አገልግሎ በሰማዕትነት ዐርፏል።
ከሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ በረከትን እንሳተፍ ዘንድ ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ጢሞቴዎስ ከላካቸው መልእክቶች ጥቂት እናንብብ።
<3 ቴዎዶስዮስ <3
በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ። ሰማዕታትም፣ ጻድቃንም፣ ሊቃውንትም፣ ነገሥታትም ተጠርተውበታልና። ዛሬ የምናከብረውም ቴዎዶስዮስ ዘየዓቢ (ታላቁ) የሚባል ሲሆን ይህን የምንለው ከትንሹ ቴዎዶስዮስ (የልጅ ልጁ ነው።) ለመለየት ነው።
ታላቁ ቴዎዶስዮስ በሮም የነገሠው በ፫፻፸ ዓ.ም አካባቢ ሲሆን ከነ ቤተሰቡ ክርስቲያን ነበር። እነዚህ ነገሮቹ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን እንዲታሰብ አድርጐታል፦
፩.በዓለም ታሪክ ክርስትና በሮም ግዛት ሁሉ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አውጇል።
፪.የቤተክርስቲያንን ትልቁን ሁለተኛ ጉባኤ ቁስጥንጥንያን በ፫፻፹፩ (፫፻፸፫) ዓ.ም አሰናድቷል።
፫.ከበጐነቱ የተነሳ የተቀደሱ ልጆችን አፍርቷል። ሙሽራው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ፣ ቅዱስ አኖሬዎስ፣ ቅዱስ አርቃዴዎስ እና ቅድስት ታኦድራ ልጆቹ ሲሆኑ አቡነ ኪሮስ ትንሽ ወንድሙ ናቸው።
ጻድቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ በ፫፻፺ ዓ.ም አካባቢ ዐርፏል።
አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል ይማረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።
ጥር ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጢሞቴዎስ (ሐዋርያና ሰማዕት - የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር)
፪.ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ (ዘቁስጥንጥንያ)
፫.ቅዱስ ጌርሎስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
፭.ቅዱስ አትናስዮስ ሰማዕት (ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተአምራቱ አሳምኖ ያስጠመቀው)
፮.አቡነ ጊዮርጊስ ዘዋሸራ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
፬.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭.አባ ሳሙኤል
፮.አባ ስምዖን
፯.አባ ገብርኤል
"መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ።
ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።"
(፩ጢሞ ፩፥፩-፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱሳት እናቶቻችን አንስጣስያና ማርያም እንተ ዕፍረት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት <3
በቀደመው ዘመን በተለይም በሮም አካባቢ ይህ ስም በጣም የተለመደ ነበር። በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳትም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አልነበረም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን ሃገረ ሮሜ እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የሁሉ መኖሪያ ነበረች።
ደጉም ሆነ ክፉው፣ ኃጥኡና ጻድቁ፣ አረማዊና ምዕመኑ፣ ጨካኙና ርኅሩኁ ወዘተ..... በአንድ ላይ ይኖሩባት ነበር። በዚህ ዘመንም ቦታዋ ብዙ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ሊቃውንትንና ጻድቃንን አፍርታለች። (ዛሬን አያድርገውና!)
ከእነዚህ ቅዱሳን አንዷ ደግሞ ሰማዕትነትን ከጽድቅና ድንግልና ጋር የደረበችው እናታችን አንስጣስያ ናት። ቅድስቲቱ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ተወልዳ ያደገችው እዚያው ሮም ውስጥ ነው። ወላጆቿ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ገና በልጅነቷ የክርስትናን ምንነት ጠንቅቃ አውቃለች።
ወጣት በሆነች ጊዜም ይህቺ ዓለም ጠልፋ እንዳትጥላት ትጠነቀቅ ነበር። ይህቺ ዓለም ወጥመዶቿ ብዙ ናቸውና። በተለይ ደግሞ መልክ ስለ ነበራትና ወላጆቿም ባለጠጐች ስለ ነበሩ እርሷ ትሕርምትን ታበዛ ነበር።
ድንግልናዋን በንጽሕና ትጠብቀው ዘንድ ጾምንና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተረች። በሒደትም በውስጧ ፍቅረ ክርስቶስ እየተቀጣጠለ በመሔዱ ይህንን ዓለም ልትተወው አሰበች። ነገር ግን ወላጆቿ "ልጃችን ለአካለ መጠን ደርሰሻልና እንዳርሽ?" አሏት።
እርሷም "እኔ ለሰማያዊው ሙሽርነት ለመንፈሳዊውም ሠርግ ተጠርቻለሁና ተውኝ።" ብላቸው ወደ ገዳም ሔደች። በዘመኑ በሮም ከተማ ዙሪያ ብዙ የደናግል ገዳማት ነበሩና ከእነዚያው ከአንዱ ገባች። እንደ ገባች ለሰውነቷ ምክንያትን ልትሠጠው አልፈለገችም።
ራሷን በጾም ትቀጣው ዘንድ በአርባ ስምንት ሰዓት (በሁለት ቀን) አንዴ ብቻ ትበላ ነበር። ምግቧም ቁራሽ ቂጣ በጨው ብቻ ነበር። ዐቢይ ጾም በደረሰ ጊዜ ግን ከእሑድ በቀር እህልን አትቀምስም ነበር። የጌታዋ ፍቅር አገብሯታልና ለሳምንት ራሷን ከምግብና ከምቾት ትከለክል ነበር።
ይህም ሲሆን ቁጭ ብላ አይደለም። በጸሎትና በስግደት እየተጋች ለደናግሉ በሙሉ እየታዘዘች ነው እንጂ። ለጥቂት ዓመታት በእንዲህ ያለ ገድል ቆይታ ከእመ ምኔቷ ጋር በዓል ለማክበር አንድ ቀን ከገዳማቸው ወጡ። በመንገድ ላይ ሳሉ አረማዊ ንጉሥ ክርስቲያኖችን ሰብስቦ ሲያሰቃይ ደረሱ።
በእርግጥ ዐይተው እያዘኑ ማለፍ ቢችሉም ቅድስት አንስጣስያ ግን አልቻለችም። የወገኖቿ ስቃይ ቢያንገበግባት በድፍረት ወደ መኮንኑ ቀርባ ዘለፈችው። "አንተ አዕምሮ የጐደለህ! እንዴት በአምላካቸው ደም የተገዙ ክርስቲያኖችን እንዲህ ያለ በደላቸው ታሰቃያቸዋለህ?" አለችው።
በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑም ወደ እርሱ አስቀርቦ "ማንን ታምኚያለሽ?" አላት። እርሷም "ሰማዩንና ምድሩን፣ ባሕሩንና የብስን የፈጠረውን ስለ ሰው ፍቅርም የሞተውንና የተነሣውን ዘላለማዊ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ።" አለችው።
እጅግ ስለ ተበሳጨም ስቃይን አዘዘባት። በገድል የተቀጠቀጠ ለምለም አካሏን በብዙ መክፈልተ ኩነኔ ወታደሮቹ አሰቃዩዋት። በመጨረሻም ሞት ተፈርዶባት በዚህች ቀን ገደሏት።
ቅድስት እናታችን አንስጣስያ የጽድቅን፣ የድንግልናን፣ የምስክርነትን አክሊል በእግዚአብሔር መንግሥት አገኘች። ይህን ሁሉ ስትጋደል ግን ዕድሜዋ ገና ወጣት ነበር።
<3 ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት <3
በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ "እንተ ዕፍረት -ባለ ሽቱ" ተብለው የሚጠሩ ሁለት እናቶች ነበሩ። ሁለቱም ስማቸው "ማርያም" ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን "ማርያም ኃጥዕት - ከኃጢአት የተመለሰች" ሁለተኛዋን ደግሞ "ማርያም እኅተ አልዓዛር - በቢታንያ የነበረችው" ብለው አበው ይጠሯቸዋል።
በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል ፲፪፥፩ ላይ ያለችው የአልዓዛር እኅት (ድንግሊቱ) ናት። ዛሬም የምናስባት ይህቺውን እናታችን ነው።
ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተምርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት። ወላጆች ባልነበሩበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል።
በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው። አልዓዛርን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ማርያምና ማርታን ደግሞ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል። ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር።
ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ። በአራተኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት ሰግዳ "እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ - አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር።" ብላ አለቀሰች።
(ዮሐ. ፲፩)
ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ። ወዲያውም በሥልጣነ ቃሉ አዝዞ አልዓዛርን አስነሳው። ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ ስድስት ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው።
(ዮሐ. ፲፪፥፩)
በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ ናርዶስ የሚሉትን የሦስት መቶ ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች። መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ..." እንዲል ምስጥ የሚያደርግ ሽታ ቤቱን ሞላው።
በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል። ቅድስት ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ" ብሎ አመስግኗታል። ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል።
ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ እናድርግ።" ብሎናል።
(ቅዳሴ ማርያም)
ቅድስት ማርያም በጌታችን ክርስቶስ በሕማሙ ጊዜም ሲቀብሩትም ነበረች፤ ትንሣኤውንም ዐይታለች።
ከጌታ ዕርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል አገልግሎት ተግታለች። ቅድስት እናታችን ማርያም እንተ ዕፍረት ዛሬ እንዳረፈች እናዘክራለን።
የእናቶቻችን ቅዱሳት አምላክ ፍቅራቸውን ያድለን። በረከታቸውንም ያብዛልን።
ጥቅምት ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት አንስጣስያ (ድንግል፣ ጻድቅት፣ ሰማዕት)
፪.ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት
፫.ቅድስት ሶስና ድንግል
፬.ቅድስት ኅርጣን ድንግል
ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
፭.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
"ሲሔዱም ወደ አንዲት መንደር ገባ። ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤቷ ተቀበለችው። ለእርሷም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት። እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች።
.....ኢየሱስም መልሶ... 'ማርያምም መልካም እድልን መርጣለች። ከእርስዋም አይወሰድባትም' አላት።"
(ሉቃ ፲፥፴፰-፵፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።
እንኳን ለታላቁ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሊቀ ጳጳሳት፣ አባ ሣሉሲና አባ ገሪማ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ <3
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያህል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም።
ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ (በሦስት መቶ ዓ.ም አካባቢ) እስክንድርያ ግብጽ ውስጥ ነው የተወለደው። ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር።
ሕፃን እያለ ለጨዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ። ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት። አትናቴዎስም ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕፃናቱ ዕጣ ተጣጣሉ።
ለአንዱ ቄስ፣ ለአንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕፃናት ይሰግዱለት ጀመር። በአጋጣሚ ሕፃናቱ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕፃኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት።
ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ጳጳሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ የሚገባውን መንፈሳዊ ትምህርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት። ከዚህ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው። ምንም ሕፃን ቢሆንም ከሊቅነቱ፣ ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና።
ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት። በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው። ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ። ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው።
ከዚህ በኋላ የእስክንድርያ (የግብጽ) ሃያኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ። ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለአርባ ስምንት ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ። ለአምስት ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ አሳልፏል።
በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል። በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ) ይጠብቃቸው ነበር። ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚህ ዘመን የተጻፈ ነው። ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በሦስት መቶ ሰባዎቹ ዓ.ም አካባቢ ዐርፏል።
ቤተ ክርስቲያን
ሊቀ ሊቃውንት፣
ርዕሰ ሊቃውንት፣
የቤተ ክርስቲያን /የምዕመናን/ ሐኪም (Doctor of the Church)፣
ሐዋርያዊ ብላ ታከብረዋለች።
ይህች ዕለት ለታላቁ ሊቅ የስደቱ መታሠቢያ ከስደቱም የተመለሰባት ቀን ናት።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን (ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ።
ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ። ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ያሳድድ ገባ። ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አትናቴዎስ ነበር።
በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ መናፍቅ ጳጳስ በግብጽ ሹሞ ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል ቅዱሱን ለስድስት ዓመታት አሰቃየው። የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግሥት ገብቶ ተናገረው።
ሁለት አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን፤ ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን) መልሰኝ።" አለው። መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ።
ቀዛፊ፣ መቅዘፊያ፣ ምግብና ውኃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው። ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ።
ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ ሌሎች መላእክት እየመገቡት በዚህች ቀን እስክንድርያ(ግብጽ) አድርሰውት ተሠውረዋል። ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል።
<3 አባ ሣሉሲ ክቡር <3
የእኒህ አባት ዜና ሕይወት ሳስበው እጅግ ይገርመኛል። የአባቶቻችን የሕይወት ፈሊጥ ምን እንደ ሆነ እንድረዳ ስላደረጉኝ በእውነቱ አመሰግናቸዋለሁ። ጻድቁ የዘመነ ከዋክብት አንድ ፍሬ ናቸው።
በነበሩበት ገዳም የሚታወቁት ግን 'የማይጾመው፣ የማይጸልየው፣ ሥራ ፈቱ መነኩሴ' በሚል ነበር። ገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩ መነኮሳት መካከል አንድም ቀን ቢሆን ሲጸልዩና ሲሰግዱ ያያቸው የለም። ሁሌ ብቻ እንደ ሞኝ ቁጭ ብለው ያኝካሉ።
በዚህ ምክንያትም ሥጋ ወደሙን ወስደው አያውቁም። አንድ ቀን ግን በገዳሙ በዓል ላይ አበምኔቱና መነኮሳቱ መከሩ። "አባ ሣሉሲን አሥረን አውለን ቢያንስ ለቁርባን እናብቃቸው።" ሲሉ ወሰኑ። በውሳኔው መሠረትም በጧት ሒደው ጻድቁን አሠሯቸው።
አባ ሣሉሲም "ፍቱኝ ቁርሴን ልብላበት?" ሲሉ ተቆጡ። መነኮሳቱ ግን "ሳትቆርብ አንለቅህም።" አሏቸው። በዚህ ጊዜ ጻድቁ ቆባቸውን አውልቀው "እመቤቴ የሰው ልጅስ ጨካኝ ነው። አንቺ ግን ርኅርኅት ነሽ።" ብለው በቆባቸው ግድግዳውን ቢመቱት ለሁለት ተሰነጠቀ።
እርሳቸውም ሁለት ክንፍ አውጥተው በረው ተሰወሩ። ባዩት ነገር የደነገጡ መነኮሳት እያለቀሱ ሦስት መቶ ጊዜ "እግዚኦ....." አሉ። በዚህ ጊዜ የጻድቁን ቆብ አገኙ። በዚህች ቆብም አጋንንትን አሳደዱ ተአምራትንም ሠሩ።
ምሥጢሩስ ምንድን ነው ቢሉ፦
አባ ሣሉሲ
፩. ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በተመስጦ (በልባቸው) ስለሚጸልዩና
፪. በጧት ተነስተው የሚያኝኩት ደረቅ ሣር እንጂ ምግብ አልነበረምና ነው።
ከውዳሴ ከንቱ መራቅ ማለት ይሔው ነው። ጻድቁ በዚህች ቀን ዐርፈው ተቀብረዋል።
እንኳን ለድንግልና ሰማዕት አርሴማ ቅድስት ወዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅድስት አርሴማ ድንግል <3
እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው። መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና።" የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል።
ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት።
ቅድስት አርሴማ ይህ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት።
ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት።
ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት።
ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ቅዱስ ጐርጐርዮስ የታላቋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው። በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት።
፩.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት።
፪.ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት።
፫.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት።
ቅዱሱ ሦስቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ። ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት። መከራው በጣም ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ፣ ይጾሙ፣ ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር።
ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው። በኋላ ግን ማኅደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኳ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ መቶ ሃያ ሰባት ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ።
በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ፤ ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው። የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ።
በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ። በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር። መከራው ግን አለቀቃቸውም። ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው።
ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት። ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ አይሆንም።" አለችው። ሊያስፈራራት ሞከረ። ዓይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው።
አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው። እጅግ ስላፈረ አስገረፋት፣ አሰቃያት፣ ዓይኗንም አወጣ። በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት።
ከነገር ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀዬራቸው።
የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ። የንጉሡ እኅት ስታለቅስ በራእይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን - ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም።" አላቸው። ወዲያውም ቆፍረው አወጡት።
ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም። ለአሥራ አምስት ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው። ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው።
የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ወደ ሃገራችን እንደ መጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል። ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ፍቅር ያላት። በዋናው ገዳሟ (ወሎ/ኩላማሶ/ስባ/ ውስጥ የሚገኝ ነው።) ጨምሮ ስሟ በተጠራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና።
ነገር ግን ወንድሞቼና እኅቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ። የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን። አባ እንጦንስ እንዳሉት "በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና።"
በዚህ ዕለት ከሰማዕቷ ጋር የመንፈስ እናቷን ቅድስት አጋታን ልናስባት ይገባናል። ይህች እናት እመምኔት ስትሆን ቅድስት አርሴማን ታስተምራት፣ ታጸናት፣ ከጐኗም ትቆምላት ነበር። ረሃቧን፣ ጥሟን፣ ስደቷን፣ መከራዋንም ሁሉ አብራት ተሳትፋለች። በፍጻሜውም አብራት ተሰይፋለች።
<3 ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ <3
የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ፣
ምድራዊው መልአክ፣
የጌታ ወዳጅ፣
የድንግል ማርያም የአደራ ልጅ፣
የንጽሕና አባት፣
ቁጹረ ገጽ፣
የፍቅር ሐዋርያ፣
የምሥጢር አዳራሽ፣
የሐዋርያት ሞገሳቸው፣
ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዛሬ ይከብራል።
ምክንያቱም "ቀዳሚሁ ቃል" (ዮሐ. ፩፥፩) ብሎ እንደ ንሥር መጥቆ ወንጌሉን በዚህች ቀን ጽፏልና።
አምላከ ቅዱሳን ለእኛ ለባሮቹ የቅድስቷን ጽናት፣ የወንጌላዊውንም ፍቅር ያድለን። በረከታቸውን ከማይጐድል እጁ አብዝቶ ይስጠን።
መስከረም ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት አርሴማ ድንግል (ሰማዕት)
፪.ቅድስት አጋታ (እመ ምኔት)
፫.መቶ አሥራ ዘጠኝ ሰማዕታት (የቅድስት አርሴማ ማኅበር)
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ነባቤ መለኮት)
፭.ቅድስት ክርስቶስ ክብራ ኢትዮጵያዊት (በዚህ ቀን ነፍሳትን ከሲዖል ታወጣለች።)
ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፬.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊት
፭.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
"በመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ። ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች። ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል። ጨለማም አላሸነፈውም።"
(ዮሐ ፩፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱሳን ሰማዕታት አባዲር ወኢራኢና ለቅድስት ሶስና ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱሳን አባዲርና እኅቱ ኢራኢ <3
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮም መንግሥት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር። የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግሥቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ፦
ፋሲለደስ፣
ገላውዴዎስ፣
ፊቅጦር፣
መቃርስ፣
አባዲር፣
ቴዎድሮስ (ሦስቱም)፣
አውሳብዮስ፣
ዮስጦስ፣
አቦሊና ሌሎቹም ነበሩ።
ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ፦
ማርታ፣
ሶፍያ፣
ኢራኢ፣
ታኡክልያና ሌሎቹም ነበሩ።
ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር። ወቅቱ ከፋርስ፣ ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ (ሞተ)።
የሮም መንግሥትም ባዶ ሆነች። ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር። ግን እነርሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ።
በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪጳዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር። ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪጳዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው። ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው።
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም። የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው። ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው። ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች።
ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ። የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ። ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው። ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግሥት እንምረጥ።" አላቸው። ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ።
ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ፤ ይጸልዩ ገቡ። ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር። ቅዱሳኑ አባዲርና ኢራኢም ከእነዚህ መካከል በመሆናቸው ተጋድሏቸውን ቀጠሉ። በተለይ ቅዱስ አባዲር በሌሊት በመካነ ጸሎቱ ሲጸልይ ያድርና በቀን ነዳያንን ይጐበኛል።
አመሻሽ ላይ ደግሞ ልብሱን ለውጦ ወደ እሥር ቤት ይሔዳል። እርሱ የአንጾኪያ ሠራዊት አለቃ ኃያል የጦር መሪ ነውና ሁሉ ይወደውና ያከብረው ነበር። በዚህም ምክንያት የእሥር ቤት ዘበኞች ምንም ከዲዮቅልጢያኖስ ከባድ ትዕዛዝ ቢኖርባቸውም ለቅዱሱ ግን ይከፍቱለት ነበር።
እርሱም ወደ እሥር ቤት ገብቶ ቁስላቸውን ጠርጐ፣ እግራቸውን አጥቦ፣ ለረሃባቸው መደገፊያ የሚሆን ማዕድም አጉርሷቸው ይወጣ ነበር። በእንዲህ ያለ ግብር ሳለ ስለ ክርስቶስ የሚሰዋበት ጊዜ ደረሰ።
አንድ ቀን በመካነ ጸሎቱ ለምስጋና ሲተጋ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት። "ስምህን ለዘላለም አከብረዋለሁ። በሰማያዊት ርስቴም አነግሥሃለሁና ከእኅትህ ኢራኢ ጋር ወደ ምድረ ግብጽ ወርዳችሁ መስክሩ።" ብሎት ለእርሷም በተመሳሳይ "ወንድምሽ የሚያዝዝሽን ሥሪ።" ብሏት መድኃኒታችን ዐረገ።
ከዚያች ቀን ጀምሮ ቅዱስ አባዲርና እኅቱ ኢራኢ ወደ ግብጽ የሚወርዱበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር። እናታቸው ግን (የቅዱስ ፋሲለደስ እኅት ናት።) ነገሩን ስትሰማ አለቀሰችባቸው። "ልጆቼ አትሙቱብኝ፤ ዲዮቅልጢያኖስንም አትናገሩት።" ስትል አማለቻቸው።
ከጥቂት ቀናት በኋላም ቅዱሱ ከእኅቱ ጋር ከሶርያ ጠፍቶ ግብጽ ገቡ። በዚያ ግን ፈተና ገጠመው። በየመንገዱ የሚያየው ሕዝቡና ሠራዊት ሁሉ "ጌታችን አባዲር" እያለ ይሰግድለት ገባ። ቀደም ሲል እንዳልነው እርሱ ኃያል የጦር መሪ የሠራዊቱም አለቃ ነውና።
ቅዱሱ ግን ወደ ክርስቶስ ሊሔድ ናፍቋልና ሠራዊቱን እና ሕዝቡን "የሚገርማችሁ ሁሉም ሰው እንዲህ ይለኛል። ግን'ኮ እኔ አንድ ተራ ምስኪን ክርስቲያን እንጂ የምትሉት ሰው አይደለሁም።" ብሎ አታለላቸው።
ቀጥሎ በክርስትናው ተከሶ ከእኅቱ ጋር ለፍርድ ቀረበና ስቃይ ታዘዘባቸው። ለሰው ዓይን የሚከብዱ ብዙ ስቃዮችን ካሳለፉ በኋላም ሞት ተፈረደባቸው። ነገር ግን አንገታቸው ከመሰየፉ በፊት መኮንኑ አርያኖስ ትክ ብሎ ሲያየው ተጠራጥሮ "ማንነትህን እንድትነግረኝ በአምላክህ አምዬሃለሁ?" አለው።
ቅዱስ አባዲርም መልሶ "አንተም ማንነቴን ካወቅክ በኋላ እኔን መግደል እንዳትተው ማልልኝ?" አለው። ማለለትም "እኔ አባዲር ነኝ።" አለው። በዚያች ቅጽበት አርያኖስ ከመደንገጡ የተነሳ መሬት ጠበበችው። በፊቱ ተደፍቶ "ወዮልኝ! ጌታዬን አባዲርን ያሰቃየሁ።" እያለ አለቀሰ። ነገር ግን ምሏልና በ፫፻ ዓ.ም አካባቢ እያዘነ በዚህች ቀን ቅዱስ አባዲርንና እኅቱን ኢራኢን አሰይፏቸዋል።
<3 ቅድስት ሶስና <3
ይህች እናት የነበረችው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በአምስት መቶ ዓመት አካባቢ ነው። እስራኤላውያን በናቡከደነጾር ተማርከው ፋርስ ባቢሎን ወርደው ሳሉ የኬልቅዩስ ልጅ የደጉ ኢዮአቄም ሚስት የሆነች እናት ናት።
ቅድስት ሶስና በስደት ሃገር እግዚአብሔርን የምታመልክ፣ ለባሏ የምትታመን፣ ለቤተሰቦቿም ኩራት የሆነች ወጣት፣ በዚያውም ላይ እጅግ የምታምር ነበረች። በዘመኑ ሕግን እናውቃለን የሚሉ ሁለት ረበናት ግን ከቅድስናዋ ሊያጐድሏት ይሹ ነበርና አልሳካላችሁ ቢላቸው በሃሰት ከሰው በወገኖቿ ፊት ሞትን አስፈረዱባት።
በፍርድ ፊት ቁማ ሳለ እርሷ በፍጹም እንባ ወደ ፈጣሪዋ ትጸልይ ነበርና እግዚአብሔር ፍርዱን ላከ። ሊገድሏት ሲወስዷት የኋላው ነቢዩ ቅዱስ ዳንኤል ያን ጊዜ ብላቴና ነበርና "እኔ ከዚህች የተባረከች ሴት ደም ንጹሕ ነኝ።" ሲል ጮኸ።
ይህንን የሰሙ ዳኞችም የፍርድ ዙፋኑን ለቀቁለት። ሁለቱን ረበናት ለየብቻቸው አድርጐ ዝሙትን ስትሠራ በየት ቦታ ላይ እንዳዩዋት ጠየቃቸው። ጌታ ሲፈርድባቸው አንዱ በኮክ ሌላኛው በሮማን ዛፍ ሥር አለ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ እነዚህን ሃሰተኛ ረበናት (መምህራን) ስለ እርሷ ፈንታ ወግረው ገደሏቸው። ቅድስት ሶስና ግን ባለ ዘመኗ ሁሉ ፈጣሪዋን አገልግላ በዚህች ቀን ዐርፋለች።
አምላከ ቅዱሳን ከክፉ ሰዎች ምክር ከአጋንንትም ሴራ በቸርነቱ ይጠብቀን። የወዳጆቹንም ጸጋ ክብራቸውን ያድለን።
መስከረም ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባዲር ሰማዕት
፪.ቅድስት ኢራኢ እኅቱ
፫.ቅድስት ሶስና እናታችን
፬.ቅዱስ ሉቃስ መነኮስ
፭.ቅዱስ ጳውፍርና
ወርኀዊ በዓላት
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
"ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች 'ዘላለም ጸንተህ የምትኖር፣ የተሠወረውን የምታውቅ፣ የሚደረገውን ሁሉ ሳይደረግ የምታውቅ ፈጣሪ ሆይ! በሐሰት እንደ ጣሉኝ አንተ ታውቃለህ። እነዚህ መምህራንም ክፉ ነገርን ባደረጉብኝ ገንዘብ የሠራሁት ኃጢአት ሳይኖር እነሆ እሞታለሁ።' አለች። እግዚአብሔርም ቃሏን ሰማት።"
(ሶስና ፩፥፵፩-፵፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱሳኑ ኤዎስጣቴዎስ፣ አንጢላርዮስ፣ ጤቅላና አባ ዮሐንስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ <3
ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ በቀድሞዋ ሮሜ ግዛት ውስጥ የጦር አለቃ፣ የከተማዋ መኮንንና እጅግ ባለጸጋ የነበረ ሰው ነው። ግን በእምነቱ አረማዊ በስሙም 'ቂዶስ' ተብሎ የሚጠራ ነበር። ምክንያቱ ባይገባውም እጅግ ቅን፣ ደግና ለምጽዋት የሚፋጠን ነበር።
እግዚአብሔር ታዲያ ይህን ሰው ወደ ቀናው ጐዳና (ወደ ክርስትና) ሊመራው ወደደና ተገለጠለት። ቂዶስ ለአደን ወጥቶ ዋሊያ ሲያድን (ያኔ ዋሊያ ከዓለም አልጠፋም ነበር። ዛሬ ግን ያለ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው።) መድኃኒታችን በዋሊያው ራስ ላይ የብርሃን መስቀልን ገልጦ ተነጋገረው።
ክርስቲያን እንዲሆንና መከራንም እንዲታገሥ አዘዘው። ቂዶስም ወደ ቤቱ ተመልሶ ለሚስቱና ለሁለት ልጆቹ የሆነውን ነገራቸው። ክርስትናን ተምረው ሲጠመቁ አበው ቂዶስን 'ኤዎስጣቴዎስ' አሉት።
ከዚህ በኋላ ክርስቶስን እያመለኩ ቆይተው ረሃብ በሃገሪቱ መጣ። ቅዱሱ ምንም መኮንንና ሃብታም ቢሆንም ገንዘቡ በምጽዋት በማለቁ ባሮቹ ተበትነው ድሃ ሆነ፤ የሚበላውንም አጣ። ከሥጋዊ ሥልጣኑም ተሻረ። እርሱ ግን ይህንን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ታገሠ።
ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ረሃቡ ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ሚስቱንና ሁለት ልጆቹን ይዞ ስደት ተነሳ። ለጉዞ በተሳፈረበት መርከብ የሚከፍለው ገንዘብ ስላልነበረው ሚስቱን ቀሙት። ልጆቹን ይዞ እያለቀሰ ከሌላ ወንዝ ደረሰ።
እንዳይሳፈር መርከበኞቹ ልጆቹን ሊቀሙት ስለሆነ ለመዋኘት ወሰነ። አንዱን ልጁን ተሸክሞ አሻግሮት ሲመለስ ትቶት የሔደውን ልጁን አንበሳ ወስዶት አገኘው። እያለቀሰና እየቸኮለ ወደ ሁለተኛው ቢመለስ ደግሞ ይህኛውንም ተኩላ ወስዶት ነበር።
ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ አንጀቱ በሃዘን ተቃጠለ። በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ መራራ ለቅሶን አለቀሰ። ነገር ግን ኢዮባዊ ሰው ነውና "እግዚአብሔር ሰጠ፤ እርሱም ነሣ።" ብሎ በእንባ ተጓዘ። በአንዲት ሃገርም ባርነት ተቀጥሮ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ኖረ።
ከብዙ ዓመታት በኋላ የረሃቡ ዘመን አልፎ የቅዱሱ ወዳጅ የነበረ ሰው በሮም ላይ በመንገሱ ወታደሮችን "ወዳጄን ኤዎስጣቴዎስን ፈልጋችሁ አምጡ።" ብሎ ላካቸው። ከአድካሚ ፍለጋ በኋላ ያ ደግ ጌታቸው በባርነት ተቀጥሮ ተጐሳቁሎ አገኙት።
ፈጥነው ወደ ሮም ከተማ ወስደው በቀደመ ክብሩ ላይ አኖሩት። እርሱ ግን ሃዘንተኛ ነበር። ከቀናት በኋላም አዳዲስ ወታደሮችን ከተለያየ ቦታ መለመለ። ከእነዚያም መካከል መልካም የሆኑትን ሁለቱን አለቆች አደረጋቸው። ሁለቱ ደግ ወጣቶችም በጣም ይዋደዱ ነበር።
አንድ ቀን እኒህ ሁለት ወጣቶች ወይን ሊገዙ ሔደው ጠባቂዋን 'ስጭን' አሏት። ሰጥታቸው እዚያው ያወራሉ። አንደኛው "ታሪኬን ልንገርህ?" ይለዋል። "እሺ" ሲለው "እኔ ወላጆች የሉኝም። ሕፃን እያለሁ በሃገራችን ረሃብ መጥቶ ሃብታችን አልቆ ስንሰደድ እናታችንን መርከበኛ ወሰዳት። አባቴ ወንድሜን ሲያሻግረው እኔን አንበሳ ወስዶ ከአንድ መንደር ጣለኝ።" አለው።
ባልንጀራው ገርሞት "ታሪካችን ተመሳሳይ ነው። እኔም እንዳንተ ሆኜ አባቴ ሲያሻግረኝ ተኩላ ወስዶ አንድ መንደር ውስጥ ጣለኝ።" አለው። ይህንን ትሰማ የነበረችው ወይን ጠባቂ "ልጆቼ!" ብላ ጮሃ አለቀሰችና ደነገጡ። እርሷም ቀርባ አቅፋቸው እያለቀሰች ነገሩን ሁሉ አስታወሰቻቸው።
ይህን ጊዜ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሰምቶ ደረሰ። ከረጅም ዓመታት በኋላ ሚስቱ አትክልት ጠባቂ ሁና ማንም ሳይነካት ሁለት ልጆቹንም አገኘ። እያለቀሱ ተቃቀፉ። እግዚአብሔርንም ፈጽመው አመሰገኑት። የሰማ ሁሉ "ዕጹብ! ዕጹብ!" አለ።
(እኛ የምናመልከው ጌታ እንዲህ ነው። ክብር ለእርሱ፣ ለድንግል እናቱና ለወዳጆቹ!)
ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቤተሰቡ በቀሪ ዘመናቸው ቤተ ክርስቲያን አንጸው በምጽዋት ኑረዋል። በመጨረሻም ዘመነ ሰማዕታት መጥቶ "ክርስቶስን አንክድም።" በማለታቸው ብዙ ተሰቃይተው አራቱም በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነዋል።
<3 ቅዱስ አንጢላርዮስ <3
ይህ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እጅግ የታወቀ ነው። በቀደመ ሕይወቱ "ሊቀ መጸብሐን - የቀራጮች አለቃ" ይሉታል። እጅግ ኃጢአተኛና ጨካኝ ሰው ነበር።
አንድ ቀን ግን አንድ የኔ ቢጤ ነዳይ ከመሰሎቹ ጋር ተወራርዶ "በእንተ ማርያም" ብሎ ቢለምነው በደረቅ ዳቦ ራሱን ገመሰው። በሌሊትም ራእይ አጋንንት ነፍሱን ሲናጠቋት መላእክት ደግሞ በዚያች ደረቅ ዳቦ አመካኝተው ሊያድኑት ሲሞክሩ አየ።
በዚያች ቅጽበትም ፍጹም ተለወጠ። መጀመሪያ ሃብት ንብረቱን በምጽዋት ጨረሰ። ቀጥሎ የሚመጸውተው ቢያጣ ነዳያንን "ሽጣችሁ ተካፈሉኝ።" አላቸውና ሸጡት። በባርነት በተሸጠበት ሃገርም በጾምና በጸሎት ተጋደለ። እረኛ ሲያደርጉትም በደረቅ በርሃ ላይ ውኃ እያፈለቀ ለምለም ሳር እያበቀለ ይመግባቸው ነበር። ዘወትርም መልአክ ያጽናናው ነበር።
በኋላ ግን ማን መሆኑ ሲታወቅበት ሸሸ። በመንገድም የከተማዋ ዘበኛ መስማትና መናገር አይችልምና እፍ ቢልበት ከቅዱሱ አፍ እንደ እሳት ያለ ነገር ወጥቶ ቢነካው ዳነ። ቅዱስ አንጢላርዮስም ቀሪ ዘመኑን በበርሃ ሲጋደል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል።
<3 ቅድስት ጤቅላ ሐዋርያዊት <3
ይህች ቅድስት እናት በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩ ቅዱሳት አንስት አንዷ ናት። ቅዱስ ጳውሎስ በእስያ የወንጌል ጉዞ ሲያደርግ ይህችን ቅድስት መቄዶንያ ላይ አግኝቷል። ቅድስት ጤቅላ ምንም ወላጆቿ አረማውያን ቢሆኑ እርሷ እስከ ሦስት ቀናት ድረስ ያለ ምንም ምግብ ቃለ እግዚአብሔርን ትሰማ ነበር።
የብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ተከታይ ሁና በእስያ ወንጌልን ሰብካለች። በብዙ ስቃይ ውስጥ ስታልፍም በኃይለ እግዚአብሔር እሳትን አጥፍታለች፤ አንበሶችም ሰግደውላታል። ቅድስት ጤቅላ ፈጣሪዋን አስደስታ በዚህች ቀን ዐርፋለች።
<3 አባ ዮሐንስ ዘደብረ ጽጌ <3
እኒህ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ በገዳም ውስጥ ሲጋደሉ ሰውነታቸው አለቀ። ቅዱሱ ከማረፉቸው በፊት የገዳሙ አባቶች ውኃ በጋን ሞልተው በላያቸው ላይ ቢያፈሱ አንድም ጠብታ ወደ መሬት ሳይወርድ ቀረ። አካላቸው ከመድረቁ የተነሳ ጠጥቶት ነበርና። ዛሬ ዕለተ ዕረፍታቸው ናት።
አምላከ ኤዎስጣቴዎስ ትእግስቱን፣
አምላከ አንጢላርዮስ ምጽዋቱን፣
አምላከ ቅድስት ጤቅላ አገልግሎቷን፣
አምላከ አባ ዮሐንስ ጽናታቸውን ያሳድርብን። የሁሉም በረከታቸው ይብዛልን።
እንኳን ለእናታችን ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት እና ቅዱስ አቡሊዲስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅድስት ማርያም <3
ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለን በስምዖን ቤት የመድኃኔ ዓለምን እግር በእንባዋ አጥባለች። በጸጉሯም አብሳ የሦስት መቶ ብር ሽቱ ቀብታዋለች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የቀደመ ኃጢአቷን ይቅር ብሎ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ደምሯታል።
(ሉቃ. ፯፥፴፮-፶)
ስለዚህች ቅድስት ሙሉ ታሪክ፦
፩.ትርጓሜ ወንጌልን
፪.ተአምረ ኢየሱስን
፫.ስንክሳርንና
፬.መጽሐፈ ግንዘትን በማንበብ ማግኘት ይቻላል።
እንተ ዕፍረት (ባለ ሽቱዋ ማለት ነው።) ማርያም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን (በዘመነ ስብከቱ) የነበረችና ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ሴት ነበረች። ግን መልክ የመልካም ነገሮች ምንጭ ሲሆን አይታይም።
በመልካቸው ማማር የጠፉና ያጠፉ ብዙ ሴቶችን ዓለማችን አስተናግዳለች። ከክሊዎፓትራ እስከ ዘመናችን "ሞዴል" ነን ባዮች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ጸጋ የሰይጣን መደሰቻ የገሃነም መንገድ አድርገውት ማየት (መስማት) እጅግ ያሳዝናል።
በአንጻሩ ደግሞ ብዙዎችን ያስደመመ መልካቸውን ንቀው ሰማያዊ ሙሽርነትን የመረጡትን ቅዱሳቱን አርሴማን፣ ቴክላን፣ ጤቅላን፣ መሪናን፣ ጣጡስን፣ ሔራኒን፣ ኢራኒን፣ አትናስያን፣ ሶፍያን፣ ኢላርያን ስናስብ ደስ ይለናል። ዛሬም ጌታ በሚያውቀው ብዙ እናቶቻችን (እኅቶቻችንም) ተመሳሳዩን በጐ ጐዳና መርጠው እየተጓዙ መሆኑን እናውቃለን።
ቅድስት ማርያምም ከፈጣሪዋ በተሰጣት ቁንጅና ክፋትን ትሠራ ዘንድ ሰይጣን ሲያገብራት "እሺ" ብላ የእሱ ወጥመድ ልትሆን ተራመደች። ለዘመናትም ዓይነ ዘማ፣ ልበ ስስ የሆኑ ወንዶችን ወደ ኃጢአት ጐዳና ማረከች።
ለመልኳ ከነበራት ስስት የተነሳም ቶሎ ቶሎ ራሷን በመጽሔት (መስታውት ማለት ነው።) ትመለከት ነበር። መቼም አምላካችን ለሁሉም የመዳን ቀን ጥሪ አለውና (የሚያስተውለው ቢገኝ) ለማርያም ጥሪውን ላከላት። ጥሪው ግን በስብከት፣ በመዝሙር ወይም በመጽሐፍ አልነበረም።
እንዳስለመደች ውበቷን ለመመልከት መስታውት ፊት ቆማ የራሷን ጸጉር፣ ግንባር፣ ዓይን፣ አፍንጫ፣ ጥርስ እየተመለከተች ተደመመች። ወዲያው ግን ይህ አካል አፈር እንደሚበላው የሚያስብ ልቡና መንፈስ ቅዱስ አምጥቶባት በጣም አዘነች። የመኖር ተስፋዋ እንዳይቆረጥ ደግሞ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ዜና ሰማች።
መወሰን ነበረባትና ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ልትሔድ ቆረጠች። በአምላኳ ፊት የሚቀርቡም ሦስት ስጦታዎችን አዘጋጀች። ሰይጣን ሊያጣት አልፈለገምና ወደ ክርስቶስ እንዳትደርስ ብዙ መሰናክልን ፈጠረባት። ግን ውሳኔዋ የእውነት ነበርና እያሳፈረችው ወደ አምላኳ ገሰገሰች።
የስምዖን ዘለምጽ በረኞችም ሊያስቀሯት አልተቻላቸውም። ወደ ውስጥ ዘልቃ የያዘችውን ሁሉ ለመድኃኒታችን ሰዋች።
፩.ከውስጧ እንባዋን፣
፪.ከአካሏ ጸጉሯንና
፫.ከንብረቷ ውድ የሆነውን ሽቱ አቀረበች።
ብዙ ወዳለችና ብዙ ኃጢአቷ ተሠርዮ ቅድስት እናታችን ሆነች። ብዙ አዝማናትን ከሐዋርያት ጋር አገልግላም በዚህች ቀን ዐርፋለች።
<3 ቅዱስ አቡሊዲስ መምህረ ኩሉ ዓለም <3
የዓለም ሁሉ መምህር፣
ባለ ብዙ ድርሳንና ተግሣጽ፣
የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ፣
ሠላሳ ስምንት ሕግጋትን የደነገገ፣
ስለ ቀናች እምነት የተጋደለ፣
መራራ ሞትን በደስታ የተቀበለ፣
የቀደመችዋ ሮም ሊቀ ጳጳሳት የነበረና ሐዋርያትን የመሰለ አባት ነው።
በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ያበራው ይህን ኮከብ ካቶሊካውያን ክደውታል። እነርሱ "አቡሊዲስ የሚባል ጳጳስ አልነበረም።" ቢሉም ምክንያታቸው ግን ከሰይጣን ነው። ሃይማኖታቸውን ከመለወጣቸው ሁለት መቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት ስለተናገረባቸውና አንድ ባሕርይን ስላስተማረ መሆኑን ዓለም ያውቃል።
አባታችን ቅዱስ አቡሊዲስ የተገደለ የካቲት ፭ ቀን ሲሆን የካቲት ፮ ሥጋው የተገኘበት ነው።
አምላከ ቅዱሳን ከቅድስት ማርያም ንስሐዋን ከአባ አቡሊዲስ ምሥጢረ ቅድስናውን ያድለን።
ከበረከተ ቅዱሳን ይክፈለን።
የካቲት ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት
፪.የዓለም ሁሉ መምህር ቅዱስ አቡሊዲስ (ብዙ መንፈሳዊ ድርሳናትን የደረሰ ሊቀ ጳጳስና ሰማዕት)
፫.ቅዱሳን አቡቂርና ዮሐንስ (ሰማዕታት)
፬.ቅድስት አትናስያና ሦስቱ ሰማዕታት ልጆቿ (ቴዎድራ፣ ቴዎፍናና ቴዎዶክስያ)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል
"አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም። እርሷ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአቷ ተሰርዮላታል። ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። እርስዋንም 'ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል።' አላት። ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው 'ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማነው?' ይሉ ጀመር። ሴቲቱንም 'እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሒጂ።' አላት።"
(ሉቃ ፯፥፵፮-፶)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ አጋቦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ አጋቦስ ሐዋርያ <3
ከሰባ ሁለቱ አርድዕት አንዱ የሆነው ቅዱሱ ሐዋርያ ሃብተ ትንቢት የተሠጠውና በዘመነ ሐዋርያት (በቀላውዴዎስ ቄሳር ጊዜ) በዓለም ላይ ከባድ ረሃብ እንደሚሆን ትንቢት የተናገረና በርካታ ክርስቲያኖችን ከረሃብና ከሞት የታደገ ትልቅ ሐዋርያ ነው።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)
በቅዱስ ጳውሎስ ላይ የሚደርሰውን መከራ በመናገሩም "ሐዋርያ ትንቢት" ተብሏል። በአገልግሎቱ ከአይሁድና ከአረማውያን ብዙዎችን ወደ ክርስትና በመሳቡ የተበሳጩ አይሁድም በዚህች ቀን ገድለውታል። በተቀደሰ ሥጋው (መቃብሩ) ላይ ብርሃን ሲወርድ ያየች አይሁዳዊት ሴትም በክርስቶስ አምና ተሰውታለች።
የአባታችን በረከት ይደርብን።
የካቲት ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አጋቦስ ነቢይ፣ ሐዋርያና ሰማዕት
፪.አባ ዘካርያስ ትሩፈ ምግባር
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ ወልደ ነጎድጓድ
፪.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫.ቅድስት ሶፊያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ
"በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ።
ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነስቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ። ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ።
ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ።
እንዲህም ደግሞ አደረጉ። በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት።"
(ሐዋ ፲፩፥፳፯-፴)
"ስለ እኛ ትጸልዩ ዘንድ ይገባችኋል። ለሁሉ መልካም ነገርን እንደምትወዱና እንደምትሹ እናምናለን።"
(ዕብ ፲፫፥፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የካቲት ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (የባሕታውያን ሁሉ አባት)
፪.ቅዱስ አባ ለንጊኖስ ሊቀ ምኔት (ደብረ ዝጋግ)
፫.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ (የሃይማኖት ጠበቃ)
፬.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ
፭.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፮.አባ ሕርያቆስ ዘሐገረ ብሕንሳ
"የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ። ተፈተኑ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ፣ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ እና ለመቶ ሃምሳው ቅዱሳን ሊቃውንት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕት <3
የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ነው።
ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት። ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ ፭ ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራእይ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት። በወለደችው ጊዜም በራእዩ መሠረት "ጴጥሮስ" አለችው።
ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተውት በሊቀ ጳጳሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ፣ ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ። ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ጴጥሮስን የግብጽ አሥራ ሰባተኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት።
ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር። ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር። ለአሥራ አራት ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ።
አርዮስን (ተማሪው ነበር።) አውግዞ ለየው። ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ። ብዙ ተአምራትንም ሠራ። በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ጵጵስናው ላይ አልተቀመጠም። በኋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ።
ሕዝቡ "ከእርሱ በፊት እኛን ግደሉን።" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ጴጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ። በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ። ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ። ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ። ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ።
የቅዱሳንን ዝክር ከማንበብ ባለፈ በስማቸው መጸለይ (ዘፀ. ፴፪፥፲፫) በምጽዋትም ማሰብ (ማቴ. ፲፥፵፩) ይገባል።
<3 መቶ ሃምሳ ቅዱሳን ሊቃውንት ጳጳሳት <3
በቁስጥንጥንያ ተሠብሥበው መናፍቃንን ያወገዙት፣ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን ያፀኑትና ጉባዔ ቁስጥንጥንያ በ፫፻፹፩ ዓ.ም ያደረጉት በዚህች ዕለት ነው።
ከወቅቱ ቅዱሳን ሊቃውንት መካከልም፦
ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ፣
ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ፣
ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪትና ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ይጠቀሳሉ።
የቅዱሳን አባቶቻችን በረከት ይደርብን።
ወርኀ የካቲትን ይባርክልን!
የካቲት ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
፪.መቶ ሃምሳ ቅዱሳን ሊቃውንት ጳጳሳት
፫.ታላቁ ቴዎዶስዮስ ጻድቅ (ንጉሠ ቁስጥንጥንያ)
፬.ሰማዕቱ አቡነ ሲኖዳ (ፍልሠታቸው)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለቅድስት ድንግል ማርያም እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ
፭.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
"ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ..... እኔ አውቃለሁ።
ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።"
(ሐዋ ፳፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃነ ዴጌ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ጻድቃነ ዴጌ <3
እነዚህ ጻድቃን ኢትዮጵያውያን ባይሆኑም ያበሩት በሃገራችን ነው። ቅዱሳኑ በቁጥር ሦስት ሺህ ሲሆኑ በዜግነት ሮማውያን ናቸው። ከሺህ አዝማናት በፊት ከሮም ግዛት ተሰባስበው እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ (አክሱም) መጥተዋል።
ቀጥለውም እዚያው አካባቢ ወደሚገኝ ገዳም ገብተዋል። ይህ ቦታ ለአክሱም ቅርብ ሲሆን በዘመነ ሐዋርያት የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ በዓት ነበር። የሐዋርያው በትረ መስቀልም እስካሁን አለች።
ጻድቃነ ዴጌ ሕጋቸው አንዲት እርሷም ፍቅር ናት። ለዘመናት በፍቅረ ክርስቶስ ታሥረው ፍቅርን ለብሰው በፍቅር ኑረዋል። ሁሌም በሃያ ዘጠኝ የጌታችንን ስም እየጠሩ ጽዋ ጠጥተዋል። ስለ ፍቅራቸውም ጌታችን ሦስት ሺህ አንደኛ ሆኖ ነዳይ መስሎ አብሯቸው ጠጥቷል።
በመጨረሻም ሦስት ሺህው በአንድነት ተሠውረዋል።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እኛንም በወዳጆቹ ጸሎት ይማረን።
ጥር ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ጻድቃን ቅዱሳን ማኅበረ ዶጌ (ዴጌ ጻድቃን)
፪.አባ ገብረ ናዝራዊ ዘቃውንት (ኢትዮጵያዊ)
፫.ቅድስት አክሳኒ ፈላሲት
፬.ቅዱስ ሰርያኮስ ሰማዕት
፭.አባ እስጢፋኖስ ገዳማዊ
፮.ከድሮዋ ሮም የተነሱ ቅዱሳት አንስት
፯.ቅዱስ ታዴዎስ ዘጽላልሽና ቅዱስ ማትያስ (ሰማዕታት)
፰.አቡነ ገብረ መርዓዊ (ልደታቸው)
ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪.ቅድስት አርሴማ ሰማዕት
፫.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እናታችን
፬.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍፃሜተ ሰማዕት
፭.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፮.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
"ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፱-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱሳን ቅዱስ ኄኖክ፣ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ እና ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ኄኖክ <3
ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ቅዱስ ኄኖክ ከአዳም ሰባተኛ ትውልድ ነው። አዳም፣ ሴት፣ ሔኖስ፣ ቃይናን፣ መላልኤል፣ ያሬድ ብለን ሰባተኛው ኄኖክ ነውና።
ቅዱሱ የማቱሳላ አባትም ነው። አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉም ሞትን ያላየ ብሔረ ሕያዋን የገባ የመጀመሪያው ሰው ሁኗል። ለአዳም ልጆችም ተስፋ ድኅነት እንዳለ ማሳያ ሁኗል። "በአቤል አፍርሆሙ ወበኄኖክ አንቅሆሙ" እንዳለ ሊቁ።
ቅዱስ ኄኖክ በ፲፬፻፹፮ ዓ.ዓ የመጀመሪያውን የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል (መጽሐፈ ኄኖክን) ከመጻፉ ባሻገር በብዙ ሥፍራ በክብር ተጠቅሶ ይገኛል።
<3 ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ <3
ይህ ቅዱስ ሐዋርያ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን መብራት ነው። ወደ ክርስትና የመጣው በ፵ዎቹ ዓ.ም አካባቢ ሲሆን አሳምኖ ለቅድስና ያበቃው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው።
በጊዜውም በነበረው ትጋትና ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል። ሆዱንም እጅግ ያመው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ሲጠራው "የምወድህ ልጄ" እያለ ነበር። በኤፌሶንም ጵጵስናን ሹሞ ሁለት መልእክታትን ልኮለታል። ቅዱስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት አገልግሎ በሰማዕትነት ዐርፏል።
ዛሬ ሥጋው ከኤፌሶን ወደ ቁስጥንጥንያ የፈለሰበት ነው። ጊዜውም ፫፻፴ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ ላይ እንደሆነ ይታመናል።
<3 ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት <3
ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም። የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው።
በሦስቱ ሰማያት ካሉት ዘጠኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው። መልአኩ እጅግ ርኅሩኅ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው። ለኖኅ መርከብን ያሳራው ከጥፋት ውኃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው።
በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው። ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እስራልዩ" ይባላል። "የእስራኤል ረዳት" እንደ ማለት ነው። ዛሬ ደግሞ የሊቀ መልአኩ ቅዳሴ ቤቱ ነው።
የቅዱሳኑ በረከት ይደርብን።
የይቅርታ ጌታ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አይተወን፤ አይጣለንም።
ጥር ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ኄኖክ ነቢይ (ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረገበት)
፪.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
፫.ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት (ከሰባቱ ሊቃናት አንዱ)
፬.ቅዱስ አባ ቢፋሞን ሰማዕት
፭.ቅዱስ ሰራብዮን ሰማዕት
ወርኀዊ በዓላት
፩.መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ
፪.አቡነ መብዓ ጽዮን
፫.አባ መቃርስ ርዕሰ መነኮሳት
፬.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፭.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
፮.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
"የተጠራችሁለት ለዚህ ነው። ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም። ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም። ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራንም ሲቀበል አልዛተም።
.....እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።"
(፩ጴጥ ፪፥፳፩-፳፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጥር ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕተ ሮሜ
፪.ቅዱሳን ባስልዮስና ጎርጎርዮስ
፫.ብፁዕ አባ ጴጥሮስ ጽሙድ (ለምጽዋት ራሱን የሸጠ አባት)
፬.ቅዱስ ሰብስትያኖስ ሰማዕት
፭.ቅዱስ አስኪላ ሰማዕት
፮.አቡነ ሕፃን ሞዐ (ልደታቸው)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፪.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፫.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፬.አቡነ አቢብ
፭.አባ አቡፋና
"የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ። ተፈተኑ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ፣ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ፣ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና።"
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ <3
<3 ልደት <3
መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው። እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ፣ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል።
በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል። በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል።
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ ቀን በ፲፪፻፮ ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን በ፲፪፻፯ ዓ/ም ነው። በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል። ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል።
<3 ዕድገት <3
የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል። ይህንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል። በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት፣ ሐዲሳትን) ተምረዋል። በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል። ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል።
<3 መጠራት <3
አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ።
የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ። "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን። ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ። ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በግርማ ዐረገ። ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም። ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ።
<3 አገልግሎት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ። በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ሁለት መልክ ነበራት።
፩ኛ.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል።
፪ኛው. ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር።
ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ። ሕዝቡንና መሳፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል።
<3 ገዳማዊ ሕይወት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል። እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በሦስት ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል።
እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለአሥራ ሁለት ዓመታት፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለሰባት ዓመታት፣ በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለሰባት ዓመታት በአጠቃላይ ለሃያ ስድስት ዓመታት አገልግለዋል።
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለሃያ ሁለት ዓመታት ቆመው ጸልየዋል። በተሰበረ እግራቸውም ስድስት ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለሰባት ዓመታት ጸልየዋል።
<3 ስድስት ክንፍ <3
ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል። ጻድቁ ምድረ እስራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ፣ እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር።
ከወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው። ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር።
ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም። በገሃድ፦
በቤተ መቅደስ ብስራቱን፣
በቤተ ልሔም ልደቱን፣
በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣
በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣
በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር።
የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ።
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አባታችንን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው።
በዚያም፦
የብርሃን ዓይን ተቀብለው፣
ስድስት ክንፍ አብቅለው፣
የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣
ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣
ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው፣
ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል።
<3 ተአምራት <3
የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው።
ሙት አንስተዋል፣
ድውያንን ፈውሰዋል፣
አጋንንትን አሳደዋል፣
እሳትን ጨብጠዋል፣
በክንፍ በረዋል፣
ደመናን ዙፋን አድርገዋል።
ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል። በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል። በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና።
<3 ዕረፍት <3
ጻድቅ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው፣ መከራን በብዙ ተቀብለው፣ እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ ቀን በ፲፫፻፮ ዓ/ም ዐርፈዋል። ጌታ፣ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል። አሥር ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል።
በዚህች ዕለት አባታችን ተክለ ሃይማኖት ለሃያ ሁለት ዓመታት የቆሙበት ቀኝ እግራቸው መሠበሩንና በአንድ እግራቸው ለሰባት ዓመታት ቆመው መጸለያቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስባለች።
አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ ምልጃ ክብራቸውን ያድለን። በረከታቸውም በዝቶ ይደርብን።
ጥር ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
፪.ቅድስት ማርያ ግብጻዊት
፫.ታላቁ አባ ቢፋ
፬.አባ አብሳዲ ቀሲስ
፭.ቅዱሳን ጻድቃነ ሐውዚን
፮.እጨጌ መርሐ ክርስቶስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ ዘዮሐንስ (ዘክብራን ገብርኤል - ጣና)
፪.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ
፫.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ
፬.ቅዱስ ሙሴ ጸሊም
፭.ቅዱስ አጋቢጦስ
፮.ሃያ አራቱ ካህናተ ሠማይ
"በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሠር አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ።
.....በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።
የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።"
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
<3 አስቀድሞ ኃይለኛ ጠንቋይ የነበረውና በኋላም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተአምሩ አሳምኖ አስጠምቆ ለሰማዕትነት ያበቃው ቅዱስ አትናስዮስ <3
ንጉሥ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተ መንግሥቱ ገብቶ በከሃዲያኑ ሰባው ነገሥታት ፊት ክርስቲያን መሆኑን በመመስከር የጌታችንን አምላክነት መሰከረ። ዱድያኖስም የቅዱስ ጊዮርጊስን ማንነቱን ከተረዳ በኋላ ‹‹አንተማ የኛ ነህ። በዐሥር አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ?›› አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም ‹‹ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን። እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም።›› አለው። በዚህ ጊዜ ዱድያኖስ እጅግ ተናዶ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን አደረሰበት። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ጌታችንን ‹‹ይህን ከሃዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰዳት።›› በማለት መከራውን ይታገስ ዘንድ ለመነው። እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ፈቃዱን ይፈጽምለት ብዙ በመከራው ሁሉ ጽናትን ሰጥቶታል። ሦስት ጊዜም ከሞት አስነሥቶታል። ቅዱስ ጊዮርጊስም የደረሱበት እጅግ አሠቃቂ መከራዎች የሰው ኅሊና ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸው ናቸው። በመጀመሪያም ዱድያኖስ በእንጨት ላይ ካሰቀለው በኋላ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው። ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሒድ አለው። ጌታችንም ቅዱስ
ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል። ዳግመኛም በሰባ ችንካሮች አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ። ሥጋውንም በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነሰነሰበት። ሥጋውም ተቆራርጦ መሬት ላይ ወደቀ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ ከፈወሰውና ‹‹ገና ስድስት ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ። ሦስት ጊዜ ትሞታለህ፤ በአራተኛውም ታርፋለህ።›› ካለው በኋላ በመከራውም ሁሉ እርሱ እንደማይለየው ነገረው።
ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚያ ካደረሰበት አሠቃቂ መከራዎች ሁሉ ድኖ ፍጹም ጤነኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ እጅግ ደንግጦ ‹‹የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ብዙ ወርቅ እሰጠዋለሁ።›› ብሎ ተናገረ። አትናስዮስ የተባለ መሠርይ አንዲትን ላም በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ስትሞት ለንጉሡ አሳየውና ቅዱስ ጊዮርጊስን እንደሚያሸንፍ ምልክት አሳየ። ንጉሡም ‹‹ያሸንፍልኛል›› ብሎ ደስ አለው። መሠርይውም ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞበት እንዲጠጣው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል። በዚህም ጊዜ ጠንቋዩ እጅግ ተገርሞ ‹‹ማረኝ›› ብሎ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግሩ ሥር ወደቀ። ዳግመኛም ‹‹አምላክህ አምላኬ ይሁነኝ።›› ብሎ ለመነው። ሰማዕቱም የዚያን መሠርይ ጠንቋይ መመለሱንና ማመኑን አይቶ የቆመባትን መሬት በእግሩ ረግጦ ውኃን አፍልቆ ወደ ጌታችን በጸሎት ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስ በመንፈስ መጣና መሠርይ የነበረውን ሰው አትናስዮስን አጠመቀው። አትናስዮስም ‹‹ከቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም።›› በማለት የጌታችንን አምላክነት በከሃድያኑ ነገሥታት ፊት መስክሮ በዛሬዋ ዕለት አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ በሰማዕትነት ዐርፏል።
የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስና በተአምሩ አሳምኖ አስጠምቆ ለሰማዕትነት ያበቃው የቅዱስ አትናስዮስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን። በጸሎታቸውም ይማረን!
(ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet)
<3 ቅዱስ ዑራኤል <3
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል፦
፪.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጓታል። በሠረገላ ብርሃን ጭኖ በክንፎቹም ተሸክሞ አስቅድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል። በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ፣ የምትለምንና የምትማልድ ሆናለች። ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች።
፪.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መርቶ አምጥቷታል። በክንፉ ተሸክሞ በአራት አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጓል።
፫.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ አፍስሷል።
፬.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል።
አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን ይፈጽምልን። ከበረከታቸውም ያድለን።
ጥር ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ እንጦንስ (የመነኮሳት አባት - የበርሐው ኮከብ ልደቱና ዕረፍቱ)
፪.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላዕክት (ለተጠሙ ጽዋዓ ልቡናን የሚያጠጣ ምሥጢር ገላጭ መልአክ)
፫.ቅዱስ ሚናስ ኤጲስ ቆጶስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፪.ቅዱስ ደቅስዮስ ኤጲስ ቆጶስ
፫.አባ ጳውሊ የዋህ
"እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ። መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል። ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።"
(ማቴ ፲፮፥፳፬-፳፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር