gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳት እናቶቻችን አንስጣስያና ማርያም እንተ ዕፍረት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት <3

በቀደመው ዘመን በተለይም በሮም አካባቢ ይህ ስም በጣም የተለመደ ነበር። በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳትም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አልነበረም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን ሃገረ ሮሜ እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የሁሉ መኖሪያ ነበረች።

ደጉም ሆነ ክፉው፣ ኃጥኡና ጻድቁ፣ አረማዊና ምዕመኑ፣ ጨካኙና ርኅሩኁ ወዘተ..... በአንድ ላይ ይኖሩባት ነበር። በዚህ ዘመንም ቦታዋ ብዙ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ሊቃውንትንና ጻድቃንን አፍርታለች። (ዛሬን አያድርገውና!)

ከእነዚህ ቅዱሳን አንዷ ደግሞ ሰማዕትነትን ከጽድቅና ድንግልና ጋር የደረበችው እናታችን አንስጣስያ ናት። ቅድስቲቱ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ተወልዳ ያደገችው እዚያው ሮም ውስጥ ነው። ወላጆቿ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ገና በልጅነቷ የክርስትናን ምንነት ጠንቅቃ አውቃለች።

ወጣት በሆነች ጊዜም ይህቺ ዓለም ጠልፋ እንዳትጥላት ትጠነቀቅ ነበር። ይህቺ ዓለም ወጥመዶቿ ብዙ ናቸውና። በተለይ ደግሞ መልክ ስለ ነበራትና ወላጆቿም ባለጠጐች ስለ ነበሩ እርሷ ትሕርምትን ታበዛ ነበር።

ድንግልናዋን በንጽሕና ትጠብቀው ዘንድ ጾምንና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተረች። በሒደትም በውስጧ ፍቅረ ክርስቶስ እየተቀጣጠለ በመሔዱ ይህንን ዓለም ልትተወው አሰበች። ነገር ግን ወላጆቿ "ልጃችን ለአካለ መጠን ደርሰሻልና እንዳርሽ?" አሏት።
እርሷም "እኔ ለሰማያዊው ሙሽርነት ለመንፈሳዊውም ሠርግ ተጠርቻለሁና ተውኝ።" ብላቸው ወደ ገዳም ሔደች። በዘመኑ በሮም ከተማ ዙሪያ ብዙ የደናግል ገዳማት ነበሩና ከእነዚያው ከአንዱ ገባች። እንደ ገባች ለሰውነቷ ምክንያትን ልትሠጠው አልፈለገችም።

ራሷን በጾም ትቀጣው ዘንድ በአርባ ስምንት ሰዓት (በሁለት ቀን) አንዴ ብቻ ትበላ ነበር። ምግቧም ቁራሽ ቂጣ በጨው ብቻ ነበር። ዐቢይ ጾም በደረሰ ጊዜ ግን ከእሑድ በቀር እህልን አትቀምስም ነበር። የጌታዋ ፍቅር አገብሯታልና ለሳምንት ራሷን ከምግብና ከምቾት ትከለክል ነበር።

ይህም ሲሆን ቁጭ ብላ አይደለም። በጸሎትና በስግደት እየተጋች ለደናግሉ በሙሉ እየታዘዘች ነው እንጂ። ለጥቂት ዓመታት በእንዲህ ያለ ገድል ቆይታ ከእመ ምኔቷ ጋር በዓል ለማክበር አንድ ቀን ከገዳማቸው ወጡ። በመንገድ ላይ ሳሉ አረማዊ ንጉሥ ክርስቲያኖችን ሰብስቦ ሲያሰቃይ ደረሱ።

በእርግጥ ዐይተው እያዘኑ ማለፍ ቢችሉም ቅድስት አንስጣስያ ግን አልቻለችም። የወገኖቿ ስቃይ ቢያንገበግባት በድፍረት ወደ መኮንኑ ቀርባ ዘለፈችው። "አንተ አዕምሮ የጐደለህ! እንዴት በአምላካቸው ደም የተገዙ ክርስቲያኖችን እንዲህ ያለ በደላቸው ታሰቃያቸዋለህ?" አለችው።
በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑም ወደ እርሱ አስቀርቦ "ማንን ታምኚያለሽ?" አላት። እርሷም "ሰማዩንና ምድሩን፣ ባሕሩንና የብስን የፈጠረውን ስለ ሰው ፍቅርም የሞተውንና የተነሣውን ዘላለማዊ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ።" አለችው።

እጅግ ስለ ተበሳጨም ስቃይን አዘዘባት። በገድል የተቀጠቀጠ ለምለም አካሏን በብዙ መክፈልተ ኩነኔ ወታደሮቹ አሰቃዩዋት። በመጨረሻም ሞት ተፈርዶባት በዚህች ቀን ገደሏት።

ቅድስት እናታችን አንስጣስያ የጽድቅን፣ የድንግልናን፣ የምስክርነትን አክሊል በእግዚአብሔር መንግሥት አገኘች። ይህን ሁሉ ስትጋደል ግን ዕድሜዋ ገና ወጣት ነበር።

<3 ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት <3

በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ "እንተ ዕፍረት -ባለ ሽቱ" ተብለው የሚጠሩ ሁለት እናቶች ነበሩ። ሁለቱም ስማቸው "ማርያም" ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን "ማርያም ኃጥዕት - ከኃጢአት የተመለሰች" ሁለተኛዋን ደግሞ "ማርያም እኅተ አልዓዛር - በቢታንያ የነበረችው" ብለው አበው ይጠሯቸዋል።

በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል ፲፪፥፩ ላይ ያለችው የአልዓዛር እኅት (ድንግሊቱ) ናት። ዛሬም የምናስባት ይህቺውን እናታችን ነው።

ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተምርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት። ወላጆች ባልነበሩበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል።

በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው። አልዓዛርን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ማርያምና ማርታን ደግሞ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል። ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር።

ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ። በአራተኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት ሰግዳ "እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ - አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር።" ብላ አለቀሰች።
(ዮሐ. ፲፩)

ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ። ወዲያውም በሥልጣነ ቃሉ አዝዞ አልዓዛርን አስነሳው። ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ ስድስት ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው።
(ዮሐ. ፲፪፥፩)

በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ ናርዶስ የሚሉትን የሦስት መቶ ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች። መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ..." እንዲል ምስጥ የሚያደርግ ሽታ ቤቱን ሞላው።

በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል። ቅድስት ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ" ብሎ አመስግኗታል። ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል።

ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ እናድርግ።" ብሎናል።
(ቅዳሴ ማርያም)
ቅድስት ማርያም በጌታችን ክርስቶስ በሕማሙ ጊዜም ሲቀብሩትም ነበረች፤ ትንሣኤውንም ዐይታለች።

ከጌታ ዕርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል አገልግሎት ተግታለች። ቅድስት እናታችን ማርያም እንተ ዕፍረት ዛሬ እንዳረፈች እናዘክራለን።

የእናቶቻችን ቅዱሳት አምላክ ፍቅራቸውን ያድለን። በረከታቸውንም ያብዛልን።

ጥቅምት ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት አንስጣስያ (ድንግል፣ ጻድቅት፣ ሰማዕት)
፪.ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት
፫.ቅድስት ሶስና ድንግል
፬.ቅድስት ኅርጣን ድንግል

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
፭.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት

"ሲሔዱም ወደ አንዲት መንደር ገባ። ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤቷ ተቀበለችው። ለእርሷም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት። እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች።
.....ኢየሱስም መልሶ... 'ማርያምም መልካም እድልን መርጣለች። ከእርስዋም አይወሰድባትም' አላት።"
(ሉቃ ፲፥፴፰-፵፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሊቀ ጳጳሳት፣ አባ ሣሉሲና አባ ገሪማ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ <3

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያህል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም።

ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ (በሦስት መቶ ዓ.ም አካባቢ) እስክንድርያ ግብጽ ውስጥ ነው የተወለደው። ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር።

ሕፃን እያለ ለጨዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ። ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት። አትናቴዎስም ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕፃናቱ ዕጣ ተጣጣሉ።

ለአንዱ ቄስ፣ ለአንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕፃናት ይሰግዱለት ጀመር። በአጋጣሚ ሕፃናቱ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕፃኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት።

ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ጳጳሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ የሚገባውን መንፈሳዊ ትምህርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት። ከዚህ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው። ምንም ሕፃን ቢሆንም ከሊቅነቱ፣ ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና።

ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት። በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው። ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ። ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው።

ከዚህ በኋላ የእስክንድርያ (የግብጽ) ሃያኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ። ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለአርባ ስምንት ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ። ለአምስት ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ አሳልፏል።

በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል። በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ) ይጠብቃቸው ነበር። ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚህ ዘመን የተጻፈ ነው። ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በሦስት መቶ ሰባዎቹ ዓ.ም አካባቢ ዐርፏል።

ቤተ ክርስቲያን
ሊቀ ሊቃውንት፣
ርዕሰ ሊቃውንት፣
የቤተ ክርስቲያን /የምዕመናን/ ሐኪም (Doctor of the Church)፣
ሐዋርያዊ ብላ ታከብረዋለች።

ይህች ዕለት ለታላቁ ሊቅ የስደቱ መታሠቢያ ከስደቱም የተመለሰባት ቀን ናት።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን (ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ።

ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ። ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ያሳድድ ገባ። ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አትናቴዎስ ነበር።

በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ መናፍቅ ጳጳስ በግብጽ ሹሞ ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል ቅዱሱን ለስድስት ዓመታት አሰቃየው። የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግሥት ገብቶ ተናገረው።

ሁለት አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን፤ ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን) መልሰኝ።" አለው። መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ።

ቀዛፊ፣ መቅዘፊያ፣ ምግብና ውኃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው። ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ።

ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ ሌሎች መላእክት እየመገቡት በዚህች ቀን እስክንድርያ(ግብጽ) አድርሰውት ተሠውረዋል። ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል።

<3 አባ ሣሉሲ ክቡር <3

የእኒህ አባት ዜና ሕይወት ሳስበው እጅግ ይገርመኛል። የአባቶቻችን የሕይወት ፈሊጥ ምን እንደ ሆነ እንድረዳ ስላደረጉኝ በእውነቱ አመሰግናቸዋለሁ። ጻድቁ የዘመነ ከዋክብት አንድ ፍሬ ናቸው።

በነበሩበት ገዳም የሚታወቁት ግን 'የማይጾመው፣ የማይጸልየው፣ ሥራ ፈቱ መነኩሴ' በሚል ነበር። ገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩ መነኮሳት መካከል አንድም ቀን ቢሆን ሲጸልዩና ሲሰግዱ ያያቸው የለም። ሁሌ ብቻ እንደ ሞኝ ቁጭ ብለው ያኝካሉ።

በዚህ ምክንያትም ሥጋ ወደሙን ወስደው አያውቁም። አንድ ቀን ግን በገዳሙ በዓል ላይ አበምኔቱና መነኮሳቱ መከሩ። "አባ ሣሉሲን አሥረን አውለን ቢያንስ ለቁርባን እናብቃቸው።" ሲሉ ወሰኑ። በውሳኔው መሠረትም በጧት ሒደው ጻድቁን አሠሯቸው።

አባ ሣሉሲም "ፍቱኝ ቁርሴን ልብላበት?" ሲሉ ተቆጡ። መነኮሳቱ ግን "ሳትቆርብ አንለቅህም።" አሏቸው። በዚህ ጊዜ ጻድቁ ቆባቸውን አውልቀው "እመቤቴ የሰው ልጅስ ጨካኝ ነው። አንቺ ግን ርኅርኅት ነሽ።" ብለው በቆባቸው ግድግዳውን ቢመቱት ለሁለት ተሰነጠቀ።

እርሳቸውም ሁለት ክንፍ አውጥተው በረው ተሰወሩ። ባዩት ነገር የደነገጡ መነኮሳት እያለቀሱ ሦስት መቶ ጊዜ "እግዚኦ....." አሉ። በዚህ ጊዜ የጻድቁን ቆብ አገኙ። በዚህች ቆብም አጋንንትን አሳደዱ ተአምራትንም ሠሩ።

ምሥጢሩስ ምንድን ነው ቢሉ፦
አባ ሣሉሲ
፩. ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በተመስጦ (በልባቸው) ስለሚጸልዩና
፪. በጧት ተነስተው የሚያኝኩት ደረቅ ሣር እንጂ ምግብ አልነበረምና ነው።
ከውዳሴ ከንቱ መራቅ ማለት ይሔው ነው። ጻድቁ በዚህች ቀን ዐርፈው ተቀብረዋል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሰማዕታት ቅዱስ እንጣዎስ እና ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ <3

ይሕ ቅዱስ በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን የሚጠላ አስቸጋሪ አረማዊ ነበር። ሃገሩ ሶርያ (ደማስቆ) ሲሆን ግብሩ ጣዖት ማምለክና መስረቅ ነበር። በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በምዕመናን ላይም ግፍን ፈጽሟል። በሥጋዊ ጉልበቱ ኃይለኛ ስለ ነበር የተፈራ ነው።

ሁልጊዜ በጠዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሔዳል። የሚሔደው ግን ንዋያተ ቅድሳትን ለመዝረፍ አንድም ካህናትን ለመደብደብ ነበር። የሚገርመው ግን የወቅቱ ምዕመናንና ካህናት ይህን ሁሉ እያደረገባቸው አይጠሉትም። ይልቁኑ ይጸልዩለት ነበር እንጂ። ምክንያቱም ክርስትና ማለት ጠላትን መውደድ ነውና።
(ማቴ. ፯)

የእግዚአብሔር ትዕግስትና የምዕመናን ጸሎት ተደምሮው አንድ ቀን ፍሬ አፈራ። እንጣዎስ እንደ ለመደው ለክፉ ሥራ ወደ ቅዱስ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ይሔዳል። ከዚያም እንደ ደረሰ ወደ ውስጥ ገብቶ የሚማታውን ተማቶ የሚዘርፈውንም ዘርፎ የተረፉትን ንዋያተ ቅድሳት በእሳት አቃጠላቸው።

እግዚአብሔር ከዚህም በላይ ታጋሽ ነውና አላጠፋውም። "ዘኢይፈቅድ ለኃጥእ ሞቶ" እንዲል የኃጢአተኛውን መመለስ እንጂ መሞቱን አይፈልግም። ለዚያም ነው ዛሬ ይሔ ሁሉ ግፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተሠራ እግዚአብሔር እንደማያይ ዝም የሚለው። ለሁሉም ቀን አለውና በፈረደ ቀን ግን በፊቱ የሚቆም አይኖርም።

እንጣዎስ ግን የሠራውን ሠርቶ እወጣለሁ ሲል አልተሳካለትም። ከበሩ አካባቢ ሲደርስ ከወደ ሰማይ አካባቢ ድምጽ ሰምቶ ቀና ሲል መላእክት እንደ እርሱ ዓይነት ኃጢአተኞችን አሰልፈው በጦርና በቀስት ሲወጓቸው ተመለከተ።

ድንገት ግን ከመላእክቱ አንዱ ዘወር ብሎ አንድ ቀስት ወደ እንጣዎስ ወረወረ (ተኮሰ)። ቀስቷ አካሉ ውስጥ ገብታለችና እንጣዎስ መሬት ላይ ወድቆ ለሞት ደረሰ። ላበቱ በግንባሩ ላይ በጭንቅ እየፈሰሰ ጮኸ።

"ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ማረኝ? ራራልኝ? ይቅር በለኝ? በድፍረት ባለ ማወቅም በድየሃለሁ። ይቅር በለኝና ላምልክህ፤ ስምህንም ልሸከም።" ሲል በጭንቀት ውስጥ ሆኖ አሰምቶ ጸለየ። በዚያ የነበሩ ምዕመናን ማን በምን እንደ ወጋው ባያውቁም ባዩት ነገር ግን እጅግ ደስ አላቸው። እነርሱም የፈለጉትና የጸለዩለት ነገር ይሔው ነበርና።

ወዲያው ግን እንጣዎስ ከሞት ጫፍ ተመልሶ ተነሳ። መጀመሪያ በቦታው የነበሩ ካህናትና ምዕመናንን "ይቅር በሉኝ?" አለ። ቀጥሎም ወደ ጳጳስ ዘንድ ሔዶ "አጥምቀኝ።" ሲል ጠየቀ። እርሱ በሚጠመቅበት ቀን ብዙ አሕዛብና ክርስቲያኖች ተሰብስበው ነበር።

እርሱ በከተማዋ ዝነኛ ነበር። ሥርዓቱ ሁሉ ተደርሶ ቅዱሱ ወደ ውኃ ገንዳው ሲገባ ሁሉ እያዩ የብርሃን ምሰሶ ከሰማይ ወረደ። ይህንን በገሃድ የተመለከቱ ከአሥር ሺህ በላይ አሕዛብ ወዲያውኑ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተጠምቀዋል።

ቅዱስ እንጣዎስ ከዚህ በኋላ ምስጉን ክርስቲያን ሆነ። ስለ ቀደመ ሕይወቱ ፈንታ ጾምን፣ ጸሎትን፣ ፍቅርን፣ ምጽዋትን ገንዘብ አደረገ። ሕይወቱም ለብዙ ሰዎች መስታዎት ሆነ። እመቤታችን ድንግል ማርያምንም ይወዳት ነበርና ወደ ቅዱሳን ማኅበር (ኢየሩሳሌም) ወስዳው በሥጋዊ አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይቻል ምሥጢርን ገልጣለታለች።

እነዚህን የቅድስና ጊዜያት በስኬት ያሳለፈው ቅዱስ እንጣዎስ መጨረሻው ሰማዕትነት ሆነ።
አረማውያን ወገኖቹና ቀድሞ የሚያውቁት ወደ ቀደመ ክፋትና ክህደት እንዲመለስ ጠየቁት። "አይሆንም።" አላቸው። በአደባባይ ለፍርድ አቅርበው ደሙ እስኪፈስ ገረፉት።

ጥርሶቹን በሙሉ በድንጋይ አረገፏቸው። ደሙና ጥርሶቹ መሬት ላይ ተዘሩ። ነገር ግን ይህ ስቃይ ቅዱሱን ከፍቅረ ክርስቶስ ሊለየው አልቻለም። አሕዛብም ተስፋ ቆርጠው በዚህች ቀን ገድለውታል። ቅዱስ እንጣዎስም ከኋለኛው ዘመን ሰማዕታት እንደ አንዱ ተቆጥሯል።

<3 ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ <3

ቅዱስ ያዕቆብ ተወልዶ ያደገው መኑፍ (ግብጽ) ውስጥ ሲሆን ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ወላጆቹ የተባረኩ ናቸውና እርሱ ሳይወለድ የነበሯቸውን ሦስት ሴቶች ልጆች "ተማሩ" ብለው ወደ ገዳም ቢያስገቧቸው በዚያው መንነው ቀሩባቸው።

በዚህ ሲያዝኑ ቅዱስ ያዕቆብ ተወልዶላቸዋል። እነርሱም በቃለ እግዚአብሔርና በጥበብ አሳድገውታል። ትንሽ ከፍ ሲል በአካባቢው ከነበረ አንድ ቅዱስ ሽማግሌ ጋር ተደብቀው ገድልን ይሠሩ ነበር። ሁሌም መልካም ምግባራትን ከመፈጸም ባለፈ ሙሉውን ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ይጸልዩ ነበር።

ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም ሁለቱ ተመካክረው ስመ ክርስቶስን በገሃድ ሰብከዋል። በዚህ ምክንያት ቅዱሱን ሽማግሌ ወዲያው ሲገድሉት ቅዱስ ያዕቆብን ግን ብዙ አሰቃይተውታል። በመጨረሻም በዚህች ቀን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀብሏል።

አምላከ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያንን ከመከራ ይጠብቅልን። ከበረከታቸውም ያሳትፈን።

ነሐሴ ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል
፪.ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ (ሰማዕት)
፫.ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ (ሰማዕት)
፬.ቅዱስ አክራጥስ ሰማዕት
፭.አባ እለእስክንድሮስ ዘቁስጥንጥንያ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
፫.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬.አባ ገሪማ ዘመደራ
፭.አባ ጰላሞን ፈላሢ
፮.አባ ለትጹን የዋህ
፯.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆጵሮስ)

"ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው። ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ። ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።"
(፩ጢሞ ፩፥፲፭-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ፈለሰት ማርያም በስብሐት ውስተ ሰማያት መላእክት ወሊቃነ መላእክት ወረዱ ለተቀብሎታ"

(እመቤታችን በምስጋና ወደዚያኛው ዓለም በተለየች ጊዜ ለአቀባበሏ መላእክትና ሊቃነ መላእክት ወረዱ።)
(ቅዱስ ያሬድ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

አምላከ ቅዱሳን ከድንግል እመ ብርሃን ፍቅር፣ ከጣዕሟ፣ ከረድኤቷ ያድለን። የወዳጆቿን ጊጋርና ጊዮርጊስን በረከትም ያብዛልን።

ነሐሴ ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም (ፍልሠቷ፣ ትንሣኤዋና ዕርገቷ)
፪.ቅዱሳን ሐዋርያት
፫.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት (ፍልሠቱ)
፬.ቅዱስ ጊጋር ሶርያዊ (ሰማዕት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
፬.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮.አባ ዳንኤል ጻድቅ
፯.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)

"ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን። እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን።
አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ። አንተና የመቅደስህ ታቦት።
ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ። ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው።
ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት....."
(መዝ ፻፴፩፥፯-፲)

"ወዳጄ ሆይ! ተነሺ። ውበቴ ሆይ! ነዪ።
..... በዓለት፣ በንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ! ቃልሽ መልካም ውበትሽም ያማረ ነውና መልክሽን አሳዪኝ። ድምጽሽንም አሰሚኝ።"
(መኃ ፪፥፲-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለንጹሐት እናቶቻችን ቅድስት እንባ መሪና እና ቅድስት ክርስጢና ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅድስት እንባ መሪና <3

ቤተ ክርስቲያን "እንቁዎቼ" ከምትላቸው ሴት ጻድቃን አንዷ ቅድስት እንባ መሪና ናት። ጣዕመ ዜናዋ ሙሉ ሕይወቷ አስገራሚም አስተማሪም ነው። ቅድስቷ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ተወልዳ ያደገች ክርስቲያን ናት። ወላጆቿ ከእርሷ በቀር ሌላ ልጅ የሌላቸው ሲሆን በአኗኗራቸውም ደግና ቅን ነበሩ።

ቅድስት እንባ መሪና ትክክለኛ ስሟ "መሪና" ነው። ምክንያቱም "እንባ መሪና" የወንድ ስም ነውና። ነገር ግን በወንድ ስም የተጠራችበት የራሱ ታሪክ አለውና እርሱን እንመለከታለን።

ቅድስት መሪና ገና ልጅ ሳለች እናቷ ማርያም ሞተችባት። ደግ አባት አንድ ልጁን በሥጋዊም በመንፈሳዊም ሳያጐድልባት አሳደጋት። ዕድሜዋ አሥራ አምስት ዓመት በሆነ ጊዜ ወደ ፊቱ አቅርቦ "ልጄ! እኔ ወደ ገዳም ስለምሔድ አንቺን መልካም ባል ላጋባሽ።" አላት።

ቅድስት መሪናም "ነፍሰ ዚአከ ታድኅን ነፍሰ ዚአየኑ ታጠፍእ - የአንተን ነፍስ አድነህ እንዴት የእኔን ትተዋታለህ? እኔም እመንናለሁ።" አለችው። አባቷ የተናገረችው ከልቧ እንደሆነ ሲያውቅ "ልጄ! ገዳም ሁሉ በአካባቢው የወንድ ብቻ ነውና ስሚኝ።" አላት።

እርሷ ግን "አባቴ! ግዴለህም ስሜን እንደ ወንድ ቀይረህ አለባበሴንም ለውጥ።" አለችው። (እንደ ወንድ ለበሰች ማለት ግን እንደ ዘመኑ ዓይነት እንዳይመስላችሁ አደራ!)

ከዚያ አባትና ልጅ ሃብት ንብረታቸውን ሸጠው ለነዳያን አካፈሉ። በፍጹም ልባቸውም መነኑ። በደረሱበት ገዳም ቅድስት መሪና በወንድ ስም "እንባ መሪና" በሚል ገባች። ቀጣዩ ሥራዋ እንደ ወንዶች እኩል መስገድ፣ መጾምና መጸለይ ነበር።

ይህችን ቅድስት ልናደንቃት ግድ ይለናል። ማንም በእርሷ አይፈተንም፤ አያውቋትምና። እርሷ ግን ወጣት ሆና አንድም ሴት በሌለበት ገዳም ጸንቶ መቆየት በራሱ ልዩ ነው። መልአካዊ ኃይልንም ይጠይቃል።

ተጋድሎዋ በጣም ስለ በዛ ወንድሞች መነኮሳት ይደነቁባት ነበር። ጺም ስለሌላትና ድምጿ ቀጭን ስለሆነ አልተጠራጠሩም። ምክንያቱም ጃንደረባ ናት ብለው አስበዋልና። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አባቷ ታሞ ከማረፉ በፊት አበ ምኔቱን ጠርቶ "ወደ ከተማ ልጄን እንዳትልክብኝ አደራ!" ብሎት ነበር።

ያም ሆኖ አንዳንድ መነኮሳት ቅሬታ በማንሳታቸው ወደ ከተማ ተላከች። ችግሩ ለተልእኮ ባደሩበት ቤት አንድ ጐረምሳ ገብቶ የአሳዳሪውን ልጅ ከክብር አሳንሷት ሔደ። ሲወጣም "ድንግልናሽን ያጠፋ ማን ነው? ካሉሽ ያ ወጣት መነኩሴ አባ እንባ መሪና ነው በይ።" አላት።

ከሦስት ወራት በኋላ የዚያች ዘማ ሴት ጽንስ በታወቀ ጊዜ ለአባቷ "አባ እንባ መሪና እንዲህ አደረገኝ።" አለችው።

አባት መጥቶ እየጮኸ መነኮሳትን ተሳደበ። አበ ምኔቱ ግራ ተጋብቶ ቢጠይቀው "የአንተ ደቀ መዝሙር እንባ መሪና ልጄን ከክብር አሳነሳት።" አለው። አበ ምኔቱ እውነት መስሎታልና ቅድስቲቱን ጠርቶ ቁጣና እርግማንን አወረደባት። በዚያች ሰዓት ተንበርክካ አንድ ነገር ወሰነች።

"ሴት ነኝ።" ብሎ መናገሩስ ቀላል ነው። ግን ደግ ናትና የእነዚያን አመጸኛ ሰዎች ኃጢአት ልትሸከም ወሰነች። ቀና ብላ "ማሩኝ ወጣትነት ቢያስተኝ ነው?" አለቻቸው። ተቆጥተው ዕለቱን እየገፉ ከገዳም አስወጧት። ከባድ ቀኖናም ጫኑባት። ከስድስት ወራት በኋላም የእርሷ ልጅ ነው የተባለ ሕፃን አምጥተው ሰጧት።

ይህኛው ግን ከባድ ፈተና ሆነባት። እንዳታጠባው አካሏ በገድል ደርቋል። በዚያ ላይ ድንግል የሆነች ሴት ወተት የላትም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት የበጋውን ሐሩር የክረምቱን ቁር ራሷ ታግሣ ለሕፃኑ ከእረኞች ወተት እየለመነች እየመገበች ሦስት ዓመታት አለፉ።

በዚህ ጊዜ ወደ ገዳሙ ከከባድ ቀኖና ጋር ተመለሰች። ሕፃኑን ስታሳድግ፣ ለገዳሙ ስትላላክ፣ ምግብ ስታዘጋጅ፣ ውኃ ስትቀዳ፣ የእያንዳንዱን ቤት ስታጸዳ ሠላሳ ሰባት ዓመታት አለፉ። ሕፃኑም አድጐ ደግ መናኝ ወጣው። (የቅድስቷ እጆች ያሳደጉት የታደለ ነው።)

በመጨረሻ ቅድስት መሪና (እንባ መሪና) ታማ ዐረፈች። እንገንዛለን ብለው ቢቀርቡ ሴት ናት። እጅግ ደንግጠው አበ ምኔቱን ጠሩት። በዙሪያዋ ከበው እንባቸውን አፈሰሱ። ጸጸት እንደ እሳት በላቻቸው። ሥጋዋን በክብር ገንዘው በአጐበር ጋርደው በራሳቸው ተሸክመው ምሕላ ገቡ።

ሙሉውን ቀን "ስለ ቅድስት መሪና ብለህ ክርስቶስ ሆይ ማረን?" ሲሉ ዋሉ። ድንገት ግን ከተባረከ ሥጋዋ "ይቅር ይበለን።" የሚል ድምጽን ሰምተው ደስ ብሏቸው ቀበሯት። እነዚያ ዝሙተኞችም ከእርሷ ይቅርታን እስካገኙበት ቀን አብደው ኑረዋል።

<3 ቅድስት ክርስጢና (ክርስቲና) ሰማዕት <3

በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳችው ሰማዕቷ ቅድስት ክርስጢና ከዋና ሰማዕታት አንዷ ስትሆን በዓለማቀፍ ደረጃም ተወዳጅ ናት። ከመነሻው የሃገረ ገዢ ልጅ ብትሆንም ቤተሰቦቿ ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ። አጥር አጥረው በር ዘግተው ከማንም ጋር ሳትገናኝ ጣዖት እንድታጥን አደረጓት።

ወጣት በሆነች ጊዜ ግን ጣዖቱን ተመለከተችው፤ መረመረችው። አምላክ እንዳልሆነም ተረዳች። ወደ ምሥራቅ ዙራ "እውነተኛው አምላክ ራስህን ግለጽልኝ?" ስትል ጸለየች።
መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ክርስትናን በልቡናዋ አሳደረባት። ቅዱስ መልአክም መጥቶ ሰማያዊ ሕብስትን መገባት።

ፈጥና ተነስታ አብርሃማዊት ቅድስት ጣዖታቱን ሰባበረች። በዚህ አባቷ ተቆጥቶ (ርባኖስ ይባላል።) በዛንጅር (ሥጋን የሚልጥ፤ የሚቆርጥ ጀራፍ ነው።) አስገረፋት። ንጽሕት ናትና ከአካሏ ደም ሳይሆን ጣፋጭ ማር ፈሰሰ።

በድጋሚ በእሳት ቢያቃጥላትም አልነካትም። ድንገት ግን አባቷ ርባኖስ ተቀሰፈ። ሌላ ንጉሥ መጥቶ በእሳትም በስለትም አሰቃያት። እርሱንም መልአክ ቀሠፈው። ሦስተኛው ንጉሥ ግን ብዙ አሰቃይቶ ጡቶቿንና ምላሷን አስቆረጣት። በመጨረሻውም በዚህች ቀን ለእፉኝት (እባብ) አስነድፎ ገድሏታል።

የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ ለእነርሱ የሰጣቸውን ጽናት አይንሳን። ከበረከታቸውም አብዝቶና አትረፍርፎ ያድለን።

ነሐሴ ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት እንባ መሪና ገዳማዊት
፪.ቅድስት ክርስጢና ሰማዕት
፫.ቅዱስ ለውረንዮስ ሰማዕት
፬.ሠላሳ ሺህ ሰማዕታት (የቅድስት ክርስቲና ማኅበር)
፭.አበው ቅዱሳን ሐዋርያት (ወላዲተ አምላክን ለመገነዝ በዚህች ዕለት ተሠብስበዋል።)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት
፫.ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)

"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።"
(፩ጴጥ ፫፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዕፀ መስቀል <3

የዕፀዋት ሁሉ ንጉሣቸው የሚሆን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ለእኛም ኃይላችን፣ ቤዛችን፣ መዳኛችን፣ የድል ምልክታችን ነው። መስቀል በደመ ክርስቶስ ተቀድሷልና አንክሮ፣ ስግደት ክብርና ምስጋና በጸጋ ይገባዋል።

ቅዱስ መስቀለ ክርስቶስ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ብዙ ተአምራትን ሠርቷል። ከእነዚህ መካከልም አንዱን በዚህ ዕለት እናዘክራለን።
ታሪኩ፤ ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በ፬፻ ዓ.ም አካባቢ በግብጽ አባ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ሳለ ቅዱስ ቄርሎስም በሊቀ ዲቁና ሲያገለግል ሳለ በእስክንድርያ ከተማ ሁለት ደሃ ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር። የቀን ሠራተኞች በመሆናቸው ከዕለት ምግብ አይተርፋቸውም ነበር።

ከሁለቱ አንዱ ፍጹም አማኝ ሲሆን ሌላኛው ግን ተጠራጣሪ ነበር።
ስለ ምን ነው ቢሉ፦
በከተማዋ ብዙ ሃብታም አይሁድ ነበሩና እነርሱን እየተመለከተ ነው። ለእርሱ ክርስትና ማለት ገንዘብ መስሎታልና ዘወትር "ለምን ክርስቶስን እያመለክን ድሃ እንሆናለን?" እያለ ያማርር ነበር።

"ያደቆነ ሰይጣን..... " እንደሚባለው አንድ ቀን ባልጀራውን "ለምን ክርስቶስን አንክደውም? (ሎቱ ስብሐት!) እርሱን ከማምለክ የተረፈን ድህነት ብቻ ነው።" አለው። ባልንጀራው ሊመክረው ሞከረ። "እግዚአብሔር አምላከ - ነዳያን ነው። ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታትም በሥጋዊ ሃብት ነዳያን ነበሩ።" ብሎ ቢለውም ሰይጣን ሠልጥኖበታልና አልሰማውም።

ያ ስሑት ደሃ ወዲያው ወጥቶ ወደ ማኅበረ አይሁድ ሔደ። እነርሱ በቁጥር ብዙ ሁነው በአንድነት ይኖሩ ነበር። "ሥራ ቅጠሩኝ።" አላቸው። "በእምነት አትመስለንምና አይሆንም።" አሉት። ያን ጊዜ ለአለቃቸው (ፈለስኪኖስ) "አንተ ሥራ ቅጠረኝ እንጂ እኔ ክርስቶስን እክዳለሁ።" (ሎቱ ስብሐት!) አለው።

ወዲያው የከተማው ሕዝብ ተጠርቶ በጉባኤ መካከል ሊያስክዱት ተዘጋጁ። በፍጥነትም መስቀል፣ ጦርና ሐሞት አዘጋጁ። ሥዕለ ስቅለቱንም አመጡ። ያን ደሃ ከሃዲም "በል - ክርስቶስ ሆይ! ካድኩህ ብለህ ምራቅህን ትፋበት፣ ሐሞቱን አፍስበት፣ በጦርም ውጋው።" (ሎቱ ስብሐት!) አሉት።

ያ ልቡ የደነቆረ መስቀለ ክርስቶስ ላይ ተፋ። ሐሞትም አፈሰሰበት። በመጨረሻ በጦር ሲወጋው ግን ድንቅ ተአምር ተገለጠ። በጦር ከተወጋው ከመስቀሉ ጐን ብዙ ደም ፈሰሰ። ለረዥም ሰዓትም አላቋረጠም። በዚህች ሰዓት በአካባቢው የነበሩ ሁሉም አይሁድ በግንባራቸው ተደፍተው ለክርስቶስና ቅዱስ መስቀሉ ሰገዱ።

ሁሉም በአንድነት "ክርስቶስ የአብርሃም አምላክ ነው። መድኃኒትም ነው።" ሲሉ እየጮሁ ተናገሩ። ባለማወቅ ስላደረጉት እነርሱ ምሕረትን ሲያገኙ ያ አዕምሮ የጐደለውን ደሃ ግን ዘወር ብለው ሲያዩት ወደ ድንጋይነት ተቀይሮ ነበር። ነፍሱንም ሥጋውንም በፈቃዱ አጠፋ።

የአይሁድ አለቃም ዓይነ ሥውር ዘመድ ነበረውና ወዲያው አምጥቶ ከደሙ ቢቀባው ዓይኑ በራ። ታላቅ ደስታም በዚያ ሥፍራ ተደረገ። ነገሩን የሰሙት ቅዱሳን ቴዎፍሎስና ቄርሎስ ሲመጡ ደሙ ከመፍሰስ አላቆመም ነበር።

በተአምሩ ደስ ተሰኝተው ከደመ ክርስቶስ ለበረከት ተቀቡ። የፈሰሰውን ቅዱስ ደም ከነአፈሩ አንስተው መስቀሉን በትከሻ ተሸክመው በፍፁም እልልታና ዝማሬ ወስደው በቤተ መቅደስ አኑረውታል። የከተማዋ ሁሉም አይሁድም በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል:።

<3 ቅዱሳን ስምዖንና ዮሐንስ <3

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ አስደናቂ ታሪክ ካላቸው ጻድቃን እነዚህ ሁለቱ ቅድሚያውን ይይዛሉ።
እርሱስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ቅዱሳኑ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሶርያ አካባቢ ተወልደው ያደጉ ክርስቲያኖች ናቸው።

ዘመዳሞች ከመሆናቸው ባሻገር አብረው ስላደጉ እጅጉን ይፋቀሩ ነበር። የዋሃንም ነበሩ። ወጣት በሆኑ ጊዜ ትልቁ ዮሐንስ ሚስት አገባ። ታዲያ አንድ ቀን ከጌታችን መቃብር ኢየሩሳሌም ደርሰው ሲመለሱ ገዳመ ዮርዳኖስ አካባቢ ደረሱ። እርስ በእርሳቸውም "ይህ ገዳምኮ የመላእክት ማደሪያ ነው።" ተባባሉ።

በዚያውም መንነው ለመቅረት አሰቡ። ፈረስና ንብረታቸውን ለዘመዶቻቸው ልከው ጸሎት አደረሱ። ፈቃደ እግዚአብሔርን ሊረዱም ዕጣ ተጣጣሉ። ዕጣውም "ወደ ገዳም ሒዱ።" የሚል ስለሆነ ተቃቅፈው ደስ አላቸው።

ወደ ገዳሙ ሲደርሱም አበ ምኔቱ አባ ኒቅዮስ ፈጣሪ አዝዞት የገዳሙን በር ከፍቶ ጠበቃቸው። ተቀብሎ ሲያስገባቸውም አንድ ደግ መነኮስ ሲያልፍ ቆቡ ቦግ ቦግ እያለ እንደ ፋና ሲያበራና መላእክት ከበውት አዩ። ወዲያውም አበ ምኔቱን "እባክህ አመንኩሰን።" አሉት።

እርሱም የአምላክ ፈቃድ ነውና በማግስቱ አመነኮሳቸው። ፍቅረ ክርስቶስ ገዝቷቸዋልና በጥቂት ዓመታት ተጋድሎ ከብቃት (ከጸጋ) ደረሱ። ሁለቱም ቆመው በፍቅር ሲጸልዩ የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ይወርድ ነበር። አካላቸውም በሌሊት ያበራ ነበር።

እንዲህ ባለ ቅድስና ለዓመታት ቆይተው ከገዳሙ ወደ ጽኑ በርሃ ሊሔዱ ስለ ፈለጉ የገዳሙ በር በራሱ ተከፈተ። አበ ምኔቱ አባ ኒቆን (ኒቅዮስ) እያነባ በጸሎት ሸኛቸው። በበርሃም በጠባቡ መንገድ በቅድስና ተጠምደው ለሃያ ዘጠኝ ዓመታት ተጋደሉ። በዚህ ሰዓት ግን ሁለቱን የሚለያይ ምክንያት ተፈጠረ።

እግዚአብሔር ቅዱስ ስምዖን ወደ ከተማ እንዲገባ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በዚያው እንዲቆይ አዘዘ። ሁለቱ ለረዥም ሰዓት ተቃቅፈው ተላቅሰው ተለያዩ። ከሃምሳ ዓመታት በላይ ተለያይተው አያውቁም ነበርና።

ቅዱስ ስምዖን ወደ ከተማ ሲገባ ክብሩን ይደብቅ ዘንድ እንደ እብድ ሆነ። በዚህ ምክንያትም የወቅቱ ከተሜዎች ይንቁት በጥፊም ይመቱት ነበር። (እባካችሁ ብዙ በየመንገዱ የወደቁ አባቶች አሉና እንጠንቀቅ!) ቅዱሱ ግን ስለ እነርሱ ይጸልይ ነበር።

በከተማዋ የነበሩ እብዶችን ሁሉንም በተአምራት ፈወሳቸው። አንድ ቀን ግን ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ደብድበውት ደከመ። የእግዚእብሔር መልአክ ወርዶ "ና ልውሰድህ።" ብሎ ዮሐንስን ከበርሃ ስምዖንን ከከተማ በዚህች ቀን ወሰዳቸው። እነሆ ብርሃናቸው ዛሬም ድረስ ለሚያምንበት ሁሉ ያበራል።

<3 ቅዱስ ባስሊቆስ ሰማዕት <3

በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ከነበሩ ስመ ጥር ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ባስሊቆስ ነው። ብዙ ጊዜ "ኃያሉ ሰማዕት" በመባልም ይጠራል። ስለ ፍቅረ ክርስቶስ በመከራ በቆየባቸው ዘመናት ሁሉ ከማመስገን በቀር ምግብ አይቀምስም ነበር።

"ለምን አትበላም?" ሲሉት "እኔ የአምላኬ ስሙና ፍቅሩ አጥግቦኛል።" ይላቸውም ነበር። አሥረው በግድ ለጣዖት ሊያሰግዱት ወደ ቤተ ጣዖት ቢያስገቡት በጸሎቱ እሳት ከሰማይ ወርዳ አማልክቶቻቸውን በልታለች። ተበሳጭተው ለቀናት የደረቀ ባላ ላይ አንጠልጥለው ቢገርፉት ደሙ ፈሰሰ።

የታሠረባት ደረቅ እንጨት ግን ለምልማ፣ አብባ፣ አፍርታ በርካቶች ተደንቀዋል። ከበረከቱም ተሳትፈዋል። ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ባስሊቆስ በዚህች ቀን ተከልሎ ጌታችንና መላእክቱ ወርደው ሲያሳርጉት ብዙ ሰው አይቶ አምኗል።

አምላከ ቅዱሳን ከፍቅረ መስቀሉ አድሎ በኃይለ መስቀሉ ይጠብቀን። የወዳጆቹን ጸጋ ክብርም ያድለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ደብረ ታቦር በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ደብረ ታቦር <3

ደብረ ታቦር በቁሙ እስራኤል ውስጥ ከሚገኙ ተራሮች አንዱ ነው። ተራራው ብዙ ታሪካዊ ዳራዎች ቢኖሩትም ክብሩ ከፍ ከፍ ያለው ግን ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ስለ ገለጸበት ነው።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደባት በዚያች በተወደደች ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምሥጢርን ይማሩ ነበር። በጊዜው ግን አበው ሐዋርያት ምሥጢር ባይገባቸው አንድም ገና መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ አልወረደም ነበርና እምነታቸው ሙሉ አልነበረም።

ጌታም አምላክነቱን በየጊዜው በቃልም በተግባርም ይገልጥላቸው ነበር። በእርግጥ ያንን ነደ እሳት ሰማያት የማይችሉትን ግሩማዊ አምላክ በትሑት ሰብዕና መመልከቱ ሊከብድ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ጌታችን ብዙ ተአምራትን በአምላካዊ ጥበቡ ሠርቷል። እጅግ ድንቅ ከሆኑት መካከል ደግሞ ቅድሚያውን ደብረ ታቦር ይይዛል።
ጌታ ስለ ምን መለኮታዊ ክብሩን በደብረ ታቦር ገለጸ ቢሉ፦
፩.ትንቢቱ ሊፈጸም (መዝ. ፹፰፥፲፪)
፪.ምሳሌው ሊፈጸም (ባርቅና ዲቦራ በሢሣራ ላይ ድልን ተቀዳጅተዋልና።)
፫.ሊቀ ነቢያት ሙሴ "ልይህ" ብሎ ከአንድ ሺህ አምስት ዓመታት በፊት ጠይቆ ነበርና እርሱን ለመፈጸም
፬.አንድነቱን ሦስትነቱን ለመግለጽ
፭.ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌ ለማሳየት
፮.ተራራውን ለመቀደስ
፯.የሐዋርያቱን ልብ ለማጽናት..... ወዘተ ነው።
ነሐሴ ፯ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልጶስ ወስዶ "የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" ብሎ ጠይቋቸው ነበር። እነርሱም የራሳቸውን ሐሳብ የሌላ እያስመሰሉ "አንዳንዶቹ ኤልያስ፣ አንዳንዶቹም ሙሴ፣ ሌሎቹም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል።" አሉት።

ኩላሊትን የሚመረምር ፈጣሪ ነውና "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ደንግጠው ዝም አሉ። የሃይማኖት አባት ባለ በጐ ሽምግልና ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በመካከላቸው ቆሞ "አንተ ውዕቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው - የሕያው እግዚአብሔር አንድያ የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ አንተ ነህ።" አለው። በዚያን ጊዜ ቃለ ብጽዓን እና የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ተሰጠው።
(ማቴ. ፲፮፥፲፫)

መጽሐፍ እንደሚል ደግሞ እንዲህ ከሆነ ከስድስተኛው ቀን በኋላ ጌታችን አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ደብረ ታቦር ወሰዳቸው። ዘጠኙን በእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ ሦስቱን (ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን) ይዟቸው ወጣ። እኒህ ሐዋርያት "አዕማድ፣ አርዕስት፣ ሐዋርያተ ምሥጢርም" ይባላሉ።

በተራራው ላይ ሳሉም ድንገት የጌታችን መልኩ ከፀሐይ ሰባት እጅ አበራ፤ ከመብረቅም ሰባት እጅ አበረቀ። "ወኮነ ልብሱ ጸዐዳ ከመ በረድ" እንዲል ከታቦር የተነሳው ብርሃነ ገጹ አርሞንኤም ደርሷል። ያንን ተመልክተው መቆም ያልቻሉት ሐዋርያቱ ፈጥነው መሬት ላይ እንደ ሻሽ ተነጠፉ።

በዚያች ሰዓት ሙሴ ከመቃብር ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጡ። አንዳንዶቹ ጌታን "ነቢይ" (ሎቱ ስብሐት) ብለውታልና ሙሴና ኤልያስ ተናገሩ፦ "ስለ ምን አንተን ነቢይ ይሉሃል፤ እግዚአ ነቢያት - የነቢያት ፈጣሪ ነህ እንጂ" እያሉ ተገዙለት፤ አመሰገኑት።

ነገር ግን በቦታው ጸንተው መቆየት አልቻሉም። መለኮታዊ ብርሃኑ ቢበዘብዛቸው ቅዱስ ሙሴም ወደ መቃብሩ ቅዱስ ኤልያስም ወደ ማደሪያው በድንጋጤ ሩጠዋል።

በዚያች ሰዓት ሊቀ ሐዋርያት ጌታን "ሠናይ ለነ ኀልዎ ዝየ። ንግበር ሠለስተ ማኅደረ አሐደ ለከ፣ ወአሐደ ለሙሴ፣ ወአሐደ ለኤልያስ - ጌታ ሆይ! በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው። በዚህም ሦስት ዳስ እንሥራ። አንዱን ለአንተ፣ አንዱንም ለሙሴ፣ አንዱን ለኤልያስ" ብሎታል።

ቅዱስ ጴጥሮስ ለራሱ ሳያስብ ለጌታና ለቅዱሳን ነቢያቱ "ቤት እንሥራ።" በማለቱ ሲመሰገን ጌታን የመጣበትን የማዳን ሥራ የሚያስተው ጥያቄ በማቅረቡ ከድካም ተቆጥሮበታል። ለሁሉም ግን ሐሳቡ ድንቅና መንፈሳዊ ነው።

እርሱ ይህንን ሲናገር መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል ወረደና ከበባቸው። አብ ከሰማይ ሆኖ "ዝንቱ ውዕቱ ወልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ - የምወደው፣ የምወልደው፣ ሕልው ሆኘ የምመለክበት የባሕርይ ልጄ እርሱ ነውና ስሙት።" ሲል ተናገረ።

ደቀ መዛሙርቱም ከፍርሃት የተነሳ በዚያች ሰዓት እንደ በድን ሁነው ነበርና ጌታችን ቀርቦ ቀሰቀሳቸው። በተነሱ ጊዜ ግን ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ተመልሶ ነበር።
(ማቴ. ፲፯ ፣ ማር. ፱ ፣ ሉቃ. ፱)

በደብረ ታቦር የጌታችንን ብርሃነ መለኮት ያዩ ሦስቱ ሐዋርያት ብቻ አይደሉም። እመ ብርሃን ካለችበት ሆና ስትመለከት ስምንቱ ሐዋርያት ደግሞ በተራራው ሥር ሆነው በተደሞ ተመልክተዋል።

ይህንን ድንቅ ብርሃነ መለኮት ያላየ ይሁዳ ብቻ ሲሆን እርሱም ስለ ክፋቱ የኢሳይያስ ትንቢት ተፈጽሞበታል። ኃጢአተኛው የእግዚአብሔርን ክብር እንደማያይ ተነግሮበታልና። "ያአትትዎ ለኃጥእ ከመ ኢይርዐይ ስብሐተ እግዚአብሔር" እንዲል።
(ኢሳ. ፳፭፥፲)

ሊቁም የደብረ ታቦርን ምሥጢር ሲያደንቅ እንዲህ ብሏል፦
"ጸርሐ አብ ኪያከ በውዳሴ
ወበርእስከ ጸለለ መንፈሰ ቅዳሴ
አመ ገበርከ እግዚኦ በታቦር ምስለ ሐዋርያት ክናሴ
መንገለ ሀሎ ኤልያስ ወኀበ ሐለወ ሙሴ
ዘመለኮትከ ወልድ ከሠትከ ሥላሴ።"

ለወዳጆቹ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠ ጌታ የእኛንም ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን። ከበዓሉ በረከትም ያሳትፈን።

ነሐሴ ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ደብረ ታቦር /ደብረ ምሥጢር/ ደብረ በረከት
፪.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት (ልደቱ)
፫.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፬.ቅዱሳን አበው ሐዋርያት
፭.አባ ጋልዮን መስተጋድል
፮.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ልደታቸው)
፯.ቅድስት ኦፍራ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬.ቅዱስ አስከናፍር
፭.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

"ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል።
ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው። እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች።"
(መዝ ፹፰፥፲፪-፲፫)

"ከስድስት ቀንም በኋላ ጌታ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ይዞ ወደ ረዥም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ። ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ። ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ጌታ ኢየሱስን፦ "ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ፣ አንዱንም ለሙሴ፣ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ።" አለ። እርሱም ገና ሲናገር እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው።
እነሆም ከደመናው፦
"በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እርሱን ስሙት።" የሚል ድምጽ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ።"
(ማቴ ፲፯፥፩-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ አባ ሞይስስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አባ ሞይስስ ጻድቅ <3

ቅዱሱ በኋላ ዘመን ከተነሱ አበው አንዱ ሲሆን ትውልዱ ከግብጽ ነው። ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ ቢሆንም ክርስቲያኖች ጠንካሮች ነበሩ። አባ ሞይስስ ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ ገና በልጅነት ወደ ትምህርት ቤት ገብቷል።

የዘመኑ ትምህርት ሁለት ወገን ሲሆን
፩ኛው የሃይማኖት ትምህርት፣
፪ኛው ደግሞ ፍልስፍና ነበር።
የጻድቁ ምርጫው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነበርና ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል። እንደሚገባ ተምሮ ስለ ነበርም ዲቁናን ሹመውት ተግቶ አገልግሏል።

ከጥቂት ዘመናት በኋላም በተሻለው ጐዳና እግዚአብሔርን ሊያገለግል ተመኘ። ይህቺን ዓለምም ይንቃት ዘንድ ወደደ። መልካም ምኞትን መፈጸም ለእግዚአብሔር ልማዱ ነውና የልቡናውን ተምኔት ፈጸመለት። ከከተማ ወጥቶ ቁራጭ ጨርቅ ለብሶ ገዳም ገባ።

በዚያም በረድእነት ያገለግል ገባ። በፍጹም ልቡ በትሕትና እግዚአብሔርን ደስ አሰኘ። በጉብዝናው ወራት ይህንን መርጧልና። ገዳሙንም ሲያገለግል ዕረፍትም አልነበረውምና በመነኮሳት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው።

ከጊዜም በኋላ "በቅተሃል።" ብለው አበው ከአሞክሮ ወደ ምንኩስና ከምንኩስና ወደ አስኬማ አሸጋግረውታል። እርሱም ለአሥራ ስምንት ዓመታት አገልግሎቱን ሳያስታጉል ወጥቶ ወርዶ ገዳሙን ረድቷል። በእነዚህ ጊዜያት በጸሎት፣ በጾምና በስግደት ይጋደል ነበር።

በጠባዩም ትእግስትን፣ ትሕትናን፣ ተፋቅሮን የሚያዘወትር ነበር። ጐን ለጐንም ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ይፋጠን ነበር። በዘመኑ የግብጽ ፓትርያርክ አባ ሚካኤል ይባሉ ነበር። አውሲም በምትባል አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ዐርፎባቸው "ማንን ልሹም?" እያሉ ይጨነቁ ነበርና እግዚአብሔር ስለ አባ ሞይስስ ገለጠላቸው።

አባ ሚካኤልም "ለሕዝቤ የሚጠቅም መልካም እረኛ አገኘሁ።" ብለው ደስ አላቸው። ጊዜ ሳጠፉም እርሱን አስጠርተው "ተሾም።" አሉት። አበው ትሕትና ሙያቸው ነውና "አይቻለኝም፤ ተውኝ ይቅርብኝ።" ሲል መለሰ።

አባ ሚካኤል ግን "የምሾምህ መቼ በሰው ፈቃድ ሆነና፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ።" ብሎ ዕለቱኑ ሹመውታል። እርሱም የአውሲም ጳጳስ ሆኗል። ቅዱሱ አባ ሞይስስም ወደ ሃገረ ስብከቱ ሔዶ አገልግሎቱን ጀመረ።

በጵጵስና ዘመኑ እንደ ከተማ ሰው መኖርን የሥጋ ምቾትን አልፈለገምና ጠባቡን መንገድ መርጧል። በገዳም ሲሰራው ከነበረው ተግባር መካከል ያቋረጠው አልነበረም። ከብቃቱ የተነሳ ለወደፊት የሚደረገውን ያውቅ ነበር። እርሱ የተነበየው ሁሉ ተፈጽሟልና።

ሕዝቡን ይመራቸው ዘንድም ተግቶ ያስምራቸው ነበር። ዘወትርም ከክፋት፣ ከኃጢአት ይጠብቃቸው ዘንድ ይጸልይላቸው ነበር። ያዘኑትን ሲያጽናና በደለኞችን ሲገስጽ ዘመናት አለፉ። አንድ ወቅት ላይም ስለ ሃይማኖቱ ታሥሮ በረሃብ ተቀጥቷል፤ ግርፋትንም ታግሷል።

ጻድቁ ጳጳስ አባ ሞይስስ እንዲህ ተመላልሶ የሚያርፍበት ቀን ቢደርስ ሕዝቡን ሰበሰባቸው። "እኔ ወደ ፈጣሪዬ እሔዳለሁና ሃይማኖታችሁንና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቁ።" ብሏቸው በትእምርተ መስቀል አማትቦ ዐረፈ። ምዕመናንም በብዙ እንባና ምስጋና ቀብረውታል። ከተቀደሰ ሥጋውና ከመቃብሩም ብዙ ተአምራት ታይተዋል።

አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ አባት በረከት ይክፈለን።

ነሐሴ ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ሞይስስ
፪.ቅዱስ አብጥልማዎስ
፫.ሦስት መቶ ሰማዕታት (የቅዱስ ፋሲለደስ ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፫.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
፬.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
፭.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት

"ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።"
(ሐዋ ፳፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለካህኑ ሰማዕት አባ ኦሪ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 ቅዱስ አባ ኦሪ ቀሲስ <3

ይህ ቅዱስ አባት የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ነው። በዘመኑ (በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ክርስቲያን መሆን ብቻውን ለሞት እንደሚያበቃ ወንጀል ይቆጠር ነበር። በጊዜው ክርስቲያን ከመሆን በባሰ መንገድ እረኛ ካህን ሆኖ መገኘት በጣም ከባድ ነበር።

ከመነሻውም ያን ጊዜ ክህነት የሚሰጠው በሕዝቡና በሊቀ ጳጳሱ ምርጫ ነበር እንጂ እንደ ዘንድሮ "እኔን ሹሙኝ።" ማለት ልማድ አልነበረም። ምዕመናንም እረኛቸውን ሲመርጡ በጉቦ፣ በዝምድና አይደለም። በርትቶ የሚያበረታቸውን ለመንጋው ራሱን አሳልፎ የሚሰጠውን ይመርጣሉ እንጂ።

ያልሆነ ሰው ለክህነት ቢመረጥ አንድም ክዶ ያስክዳል ሲቀጥልም ለሕዝቡ መሰናክል መሆኑ አይቀርም። በጊዜው (በዘመነ ሰማዕታት) የነበሩ ካህናት የቤት ሥራቸውም ማስተማር ብቻ አልነበረም። በድፍረት በምዕመናን ፊት አንገታቸውን ለሰይፍ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር እንጂ።

ይህንን በገሃድ መፈጸም ከቻሉ አበው አንዱ ደግሞ አባ ኦሪ ቀሲስ ናቸው። ቅዱሱ ተወልደው ባደጉባት ሃገረ ስጥኑፍ (የግብጽ አውራጃ ናት።) መጻሕፍትን የተማሩ፣ ተወዳጅና ደግ ሰው ነበሩ።

አባ ኦሪ ገና በወጣትነት ቀዳሚ ግብራቸው መንኖ ጥሪት (ምናኔ) ነበር። በንጽሕናቸው ደስ የተሰኙ ምዕመናንም "ቅስና ተሹመህ ምራን፤ አስተምረን።" ቢሏቸው አበው ውዳሴ ከንቱን አይፈልጉምና "አይሆንም።" አሉ።

ነገሩ ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረና አባ ኦሪ ቅስናን ተሹመው ያገለግሉ ገቡ። ሕዝቡን በማስተማር፣ በመምከር፣ ደካማውን በማጽናት ብዙ ደክመዋል።
ከቅድስናቸው የተነሳ ቅዳሴ ሊቀድሱ ሲገቡ ጌታችን በገሃድ ይገለጥላቸው ነበር። ሠራዊተ መላእክትም ከበው ይነጋገሯቸው ነበር።

ሥጋውን ደሙን በማቀበልም ተግተው ዘመናት አለፉ። ቆይቶ ግን ያ በዜና ይሰሙት የነበረ መከራ (ሰማዕትነት) በደጃቸው ደረሰ። በጊዜው ብዙ ሰው በሰማዕትነት አለፈ። አባ ኦሪም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ገብተው ስለ ራሳቸውና ሕዝቡ ጽናትን፣ ደኅንነትን ለመኑና ከቤተ ክርስቲያን ወጡ።

በቀጥታ የሔዱትም ወደ ዐውደ ስምዕ (የምሥክርነት አደባባይ) ነበር። በመኮንኑ ፊት ቀርበው "ክርስቶስ አምላክ፣ ፈጣሪ፣ የሁሉ ጌታ ነው። የእናንተ ጣዖት ግን ጠፊ ረጋፊ ወርቅ፣ ብር፣ እንጨትና ድንጋይ ነው።" ሲሉ በድፍረት ተናገሩ።

መኮንኑም ከአነጋገራቸው የተነሳ ተቆጥቶ ሥቃይን አዘዘባቸው። ወታደሮቹ ይሆናል ያሉትን ማሰቃያ ሁሉ አባ ኦሪ ላይ ሞከሩ። በኋላም ወደ ጨለማ እሥር ቤት ወስደው ጣሏቸው። በእሥር ቤት ውስጥም ድውያንን ፈወሱ ተአምራትን ሠሩ።

ይህንን ዜና የሰሙ አሕዛብ ብዙ ድውያንን ሰብስበው መጡ። ቅዱሱም ሁሉን በጸሎታቸው ፈወሱ። በዚህ ምክንያትም ብዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና መጥተዋል። በክርስቶስ አምነውም ለክብር በቅተዋል።

ቅዱሱንም ከእሥር ቤት አውጥተው ብዙ ካሰቃዩዋቸው በኋላ በዚህች ቀን ገድለዋቸው ሰማዕትነትን አግኝተዋል። በአክሊለ ጽድቅ ላይ አክሊለ ካህናትን በአክሊለ ካህናትም ላይ አክሊለ ሰማዕታትን ደርበዋል።

አምላከ ቅዱሳን በአባቶቻችን ጽናት ያጽናን። ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን።

ነሐሴ ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ኦሪ ቀሲስ (ሰማዕት)
፪.አባ ጲላጦስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
፫.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
፬.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
፮.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

"ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ። በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?
..... እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን። ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።"
(፩ቆሮ ፲፥፲፬-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ሚ ቡርክት ወቅድስት ይእቲ
ሰዓተ ትፍሥሕት ሐና ዘጸገየተኪ ባቲ
ወፈረየኪ ለሕይወት ኢያቄም መዋቲ
እሴብሕ ተአምረኪ ርግብየ አሐቲ
ወድኀኒተ ኲሉ ዓለም እስመ ኮንኪ አንቲ"

(ሐና አንቺን የፀነሰችባት የደስታ ቀን ምን ያህል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ ሟች ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን ያፈራባት ቀን ምን ያህል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ አንዲቱ ርግቤ ማርያም አንቺ የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ሆነሻልና ታምርሽን አመሰግናለሁ።)
(አባ ጽጌ ድንግል ወአባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅድስት እናታችን ማርያም መግደላዊት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅድስት ማርያም መግደላዊት <3

ይህችን ቅድስት "ማርያም" ያሏት ወላጆቿ ሲሆኑ "መግደላዊት" እያሉ የጠሯት ደግሞ ሐዋርያት (ወንጌላውያን) ናቸው። ለምን እንዲህ ብለው ጠሯት ቢሉ፦ በዘመኑ "ማርያም" የሚባሉ ብዙ ሴቶች ነበሩና ከእነርሱ ለመለየት ነው። አንድም ሃገሯ ከእስራኤል አውራጃዎች በአንዱ (በመግደሎን) ተወልዳ ያደገች ናትና።

ማርያም መግደላዊት ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ነበረችና ሰዎች ያደንቋት ወንዶች ይከተሏት ነበር። በዚህም ሰባት አጋንንት ተጠግተው ሰባት ዓይነት ኃጢአትን ያሠሯት ነበር። በተለይ ደግሞ በዝሙት፣ በትውዝፍት (ምንዝር ጌጥ)ና ትዕቢት በእጅጉ የታወቀች ነበረች።

በእንዲህ ያለ ግብር ጸንታ ለዘመናት ኖረች። በዚያ ወራት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን ተዋሕዶ ያስተምር ነበርና ስለ እርሱ ሰማች። "ጌታ ኃጥአንን አይጸየፍም (ይቀበላል) አጋንንትንም ያስወጣል።" ብለውም ነገሯት። ጥሪው የእግዚአብሔር ነውና ማርያም መግደላዊት አልዘገየችም።

ወደ እርሱ ሔዳ ጌታ ባያት ጊዜ ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና አቀረባት። በቸርነቱም ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ የሞሉትን ሰባት የአጋንንት ነገድ አስወጣላት። በዚያች ሰዓት ዕለቱኑ እንደተወለደ ሕፃን ከነበረባት ችግር ሁሉ ንጹሕ ሆነች። ጌታም ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ትሆን ዘንድ መርጦ ተከታዩ አደረጋት።

ቅድስት ማርያም ከዚህች ቀን ጀምሮ ፍጹም ተቀየረች። እርምጃዋ ሁሉ የተባረከና የንጽሕና ሆነ። ጌታን እስከ ዕለተ ሕማሙ ድረስ በመዓልትም በሌሊትም በቅን አገለገለችው።
ጌታችን ስለ እኛ መከራን በተቀበለባት በዚያች ዕለተ ዓርብም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ከጐኑ ነበረች።

ከግርፋቱ እስከ ስቅላቱ እያለቀሰች ተከትላዋለች። በእግረ መስቀሉ ያለቅሱ ከነበሩ ቅዱሳት አንስትም አንዷ እርሷ ነበረች።
(ዮሐ. ፲፱፥፳፭)
ቅዱሳኑ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጌታን ሲቀብሩትም ከእኅቶቿ ጋር አብራ ተከትላ አይታለች።

እሑድ በሌሊት ገናም ሳይነጋ መቃብሩን ታይ ዘንድ ሽቱም ልትቀባ ወደ ጐልጐታ ገሠገሠች። ፍጹም የአምላክ ፍቅር አድሮባታልና ግርማ ሌሊቱንና የአይሁድ ጭፍሮችን አልፈራችም። ጌታችንም ከእመቤታችን ቀጥሎ ከፍጥረት ወገን ትንሣኤውን ያየች የመጀመሪያዋ ሰው ትሆን ዘንድ አደላት።

በመቃብሩ ራስጌና ግርጌም ሁለት መላእክትን (ሚካኤልና ገብርኤልን) ተመለከተች። ዘወር ስትል ደግሞ የክብርን ባለቤት አየችው። አላወቀችውምና "ማርያም" አላት። "ረቡኒ-ቸር መምህር ሆይ" ብላ ሰገደችለት።

ጌታም "ሑሪ ኀበ አኀውየ ወበሊዮሙ..... ሒደሽ ለደቀ መዛሙርቴ በያቸው....." ብሎ የትንሣኤው ሰባኪ አደረጋት። "ወሖረት ወነገረቶሙ ለአርዳኢሁ..... " እንዲል ትንሣኤውን ለደጋጉ ሐዋርያት ሰበከችላቸው።

ቅድስት ማርያም መግደላዊት ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ለአርባ ቀን መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምራለች። በዕርገቱ ተባርካ በበዓለ ሃምሳ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ተካፍላለች። በአዲሲቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ልዩ አገልግሎት ነበራት።

ቅዱሱ እስጢፋኖስ ስምንት ሺህውን ማኅበር ሲመራ ሴቶችን ታስተዳድርለት ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ቅድስቲቱ የቅዱሳን ሐዋርያት መጋቢ ነበረች። በዘመኑ መንፈስ ቅዱስ የሚባርከውን አጋፔ (የፍቅር ማዕድ) የምታዘጋጀው እርሷ ነበረች።

እንዲያውም አንዴ የሚበላ ጠፍቶ ለሐዋርያት ማዕድ ፍለጋ በሔደችበት እግሯ ቆስሎና ደምቶ መመለሷ ይነገራል። እንዲህ አድርጋ ያዘጋጀችውን ማዕድ ቅዱስ መልአክ ወርዶ ወደ ሰማይ ወስዶታል። ለቅዱሳን ሐዋርያትም እያመጣ ይመግባቸው ነበር።

እናታችን ማርያም መግደላዊት በስብከተ ወንጌልም የተመሰከረላት ነበረች። የመጀመሪያዋ የሐዲስ ኪዳን ዲያቆናዊት ሴት ስትሆን ክርስትናንም ተዟዙራ ሰብካለች። ስለ ቅዱስ ስሙም ሽሙጥን፣ ስድብን፣ መንገላታትንና ግርፋትን ታግሳለች።

በተለይ አይሁድ ብዙ አሰቃይተዋታል። ቅድስቷ እናታችን መልካሙን ገድል ተጋድላ በበጐ እድሜ በዚህች ቀን ሔዳለች። በዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ (ከአንዳንዶቹ በቀር) ያከብሯታል።

<3 ቅድስት ኢየሉጣ ዘቂሣርያ <3

በቀድሞው የግሪክ ግዛት (ቂሣርያ ውስጥ) በዘመነ ሰማዕታት አካባቢ የነበረችው ቅድስት ኢየሉጣ ክርስትናን የወረሰችው ከወላጆቿ ነው። ገና ወጣት እያለች ወላጆቿ በማረፋቸው የሃብታቸው ወራሽ ሆነች።

ነገር ግን አንድ ክፉ ሰው መጥቶ ሃብቷን ነጠቃት። በዚህ አዝና "የዳኛ ያለህ" ልትል ወደ ፍርድ ቤት ስትሔድ የጠበቃት ግን የሚገርም ነበር። የተገፋችው እርሷ ተከሳሽ ገፊው ደግሞ ከሳሽ ነበር። የክሱ ጭብጥ ደግሞ "ክርስቲያን ነሽ።" የሚል ነበር።

በወቅቱ በመኳንቱ ፊት ክርስትናዋን ብትክድ በቀጥታ ሃብቷን ማግኘት ትችል ነበር። እርሷ ግን ለአፍታ አሰበች። "እንዴት ዘላለማዊ ሃብቴን (ሃይማኖቴን) በኃላፊው ንብረት እለውጣለሁ።" ብላ ሁሉም እየሰሙ ጮክ ብላ "ክርስቲያን ነኝ።" አለች።

ወዲያውም ሞት ተፈርዶባት ተገደለች። ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ስለ ሰማዕታት በጻፈው ድርሳን ላይ በስፋት አመስግኗታል። ለሴቶችም ታላቅ ምሳሌ ናት ብሏታል።

ቅዱሳት እናቶቻችንን ያጸና ቸር አምላካቸው እኛንም በሃይማኖትና በምግባር ያጽናን። ከበረከታቸውም አብዝቶ ያድለን።

ነሐሴ ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ማርያም መግደላዊት (ከሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት)
፪.ቅድስት ኢየሉጣ ሰማዕት (ዘቂሣርያ)
፫.አባ ዊጻ (የታላቁ ሲኖዳ ደቀ መዝሙር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"ጌታ ኢየሱስም፦ "ማርያም" አላት። እርሷ ዘወር ብላ በእብራይስጥ፦ "ረቡኒ" አለችው። ትርጓሜውም "መምህር ሆይ!" ማለት ነው። ጌታ ኢየሱስም፦ "ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ። ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሔደሽ.... ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው።" አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።"
(ዮሐ ፳፥፲፮-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ ንጉሥ ሕዝቅያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 ቅዱስ ሕዝቅያስ <3

ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን ከመድኃኒታችን ክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመታት በፊት ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር። ደጋጉ ዳዊትና ሰሎሞን ካረፉ በኋላ የሕዝቅያስን ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእስራኤል ላይ አልነገሠም። ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም ነበር።

ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሣበት። ወደ አካባቢውም መጥቶ ከቦ አስጨነቀው። ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር። በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከመቶ ሰማንያ አምስት ሺህ በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት።

"እገብርልሃለሁ፤ የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ። ነገር ግን ሃገሬን አታጥፋ። ኢየሩሳሌምን አታቃጥል፤ ሕዝቤንም አትግደል።" በሚል ለመነው። እጅ መንሻ ግብሩንም ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት።

ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእስራኤልን አምላክ፣ ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ። ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ ማነው? ሕዝቡንም እግዚአብሔር ያድናል ብለህ አታታልላቸው።" ሲል ላከበት። ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ።

መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ። ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ።

በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ አንደበት እንዲህ አለ፦ "ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ።"

በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ። ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ። በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል።

በድንጋጤ ወደ ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት። ትዕቢተኛው ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ። ቅዱስ ሕዝቅያስ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖት የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት።
(፩ነገ. ፲፰፥፲፫ ፤ ፲፱፥፩)

ቅዱስ ሕዝቅያስ የነሐስ እባቡን በማጥፋቱ ሕዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በመመለሱ ቢደነቅም ሰው ነውና አንዲት ጥፋት አጠፋ። በዘመኑ ታላቁ ነቢይ ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ነበረና ሐረገ ትንቢትን ያፈስ ነበር። ከተናገራቸው ትንቢቶችም አንዱ "ድንግል ትጸንሳለች። ወንድ ልጅም ትወልዳለች።" የሚል ነበር።
(ኢሳ. ፯፥፲፬)

በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ክፉ መካሪዎች ቀርበው ንጉሡን በውዳሴ ከንቱ ጠለፉት። "ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ። እንዳንተ ያለ ማንም የለም። ነቢዩ የተናገረው ትንቢትም እኮ ላንተ ነው። 'ድንግል' የተባለች ኢየሩሳሌም ስትሆን 'ወልድ - ወንድ ልጅ' የተባልክ ደግሞ አንተ ነህ።" አሉት።

ይህንን ጠማማ ትርጉም እህ ብሎ የሰማቸው ቅዱስ ሕዝቅያስ አልወቀሳቸውም። ይልቁኑ ልቡ ወደ እነርሱ አዘነበለ እንጂ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ኢሳይያስን ላከው።
ነቢዩም በቀጥታ መጥቶ ንጉሡን አለው፦ "ትሞታለህ እንጂ አትተርፍምና ቤትህን ሥራ።"

ወዲያውኑ ሕዝቅያስ ታመመ፤ ደከመ። ነገር ግን ፊቱን ወደ ቤተ መቅደስ አዙሮ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመረ። አባቶቻችን ለየት የሚያደርጋቸው ይኼ ነው። በቅድስና ኑረው ሰው ናቸውና ይሳሳታሉ። ነገር ግን ንጹሕና ፍጹም ንስሐን ከማቅረብ አያቋርጡም።

ንጉሡ ቅዱስ ሕዝቅያስ ወደ ፈጣሪ፦ "ጌታ ሆይ! እንደ ቸርነትህ በፊትህ በቅን መንገድ መሔዴን አስብና ይቅር በለኝ።" ሲል ተማጸነ። ይህ ሲሆን ቅዱስ ኢሳይያስ ገና ከንጉሡ አካባቢ አልራቀም ነበርና የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ።

ሕዝቅያስን በለው፦ "ጸሎትህን ሰምቼ ስለ ባለሟሌ ስለ ዳዊት ብዬ ምሬሐለሁ። በዘመንህም ላይ አሥራ አምስት ዓመታትን ጨምሬልሃለሁ በለው።" አለው። ነቢዩም ወደ ንጉሡ ተመልሶ ይህንኑ ነግሮ "እስከ ሦስት ቀን ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ ድነህ ትመለሳለህ።" አለው።

ቅዱስ ሕዝቅያስ "ይህ እንደሚደረግ በምን አውቃለሁ?" አለው። ተጠራጥሮ ግን አይደለም። ድንቅ ተአምር ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ። ኢሳይያስም ፀሐይን ዓለም እያየ አሥር መዓርጋትን ወደ ኋላ መለሳት። በወቅቱ ይህ ተአምር በመላው ዓለም ታይቶ ተሰምቶም ነበርና ሕዝቅያስ ከፍ ከፍ አለ።

በቅን የሔደ እግዚአብሔርም የወደደው እንዲህ ነው። የዓለም ነገሥታት ሁሉ ለሕዝቅያስ አዘነበሉ፤ ገበሩለትም። ለእርሱ ጌታ ድንቅ ነገርን አድርጐለታልና።

ቅዱስ ሕዝቅያስ በተጨመሩለት ዘመናት ሁሉ እግዚአብሔርን አመለከ። በፊቱም በቅን ተጓዘ። ከክርስቶስ የዘር ሐረግም በቀጥታ ተቆጠረ። (ማቴ. ፩፥፲)
ለአሥራ አምስት ዓመታት ሕዝቡን አስተዳድሮ በዚህች ቀን እድሜ ጠግቦ ዐርፏል። በእርሱ ዙፋን ላይም ልጁ ምናሴ ተተክቷል።

<3 አባ ማቴዎስ ገዳማዊ <3

እኒህ ቅዱስ ሰው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፋርስ አካባቢ የነበሩ ጻድቅ ናቸው። በወቅቱ ምንኩስና በአካባቢው ባለመስፋፋቱ ወደ ዱር እየወጡ የሚኖሩ አበው ነበሩና አባ ማቴዎስ አንዱ ናቸው። እርሳቸው በበርሃ ልብሳቸው አልቆ አካላቸው የሚሸፈነው በጸጉራቸው ነበር።

የአቶር ንጉሥ የሰናክሬም ልጅ መርምሕናምን (እጅግ ታላቅ ሰማዕት ነው።) ያሳመኑትና ያጠመቁት እርሳቸው ናቸው። እኅቱን ሣራንም ከለምጿ አንጽተው ወደ ክርስትና መልሰዋል። በዚህ ምክንያትም የፋርስ አውራጃ የሆነችው አቶር በሙሉ የክርስቲያኖች ቤት ሆናለች። አባ ማቴዎስ ከዘመናት ተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፈዋል።

አምላከ ቅዱሳን እድሜ ለንስሐ፣ ዘመን ለፍስሃ አይንሳን። የጻድቃኑ በረከትም ይደርብን።

ነሐሴ ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሕዝቅያስ ጻድቅ (ንጉሠ ይሁዳ)
፪.አባ ማቴዎስ ገዳማዊ
፫.ቅዱስ ዳዊት ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ (ወንጌላዊው)
፪.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

"አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል። በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል።
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው። የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም።
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና። ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ።
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም። ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ።
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው።"
(መዝ ፳፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳት እናቶቻችን አትናስያና ኢዮጰራቅስያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅድስት አትናስያ <3

የዚህች ቅድስት ሕይወት በብዛት የእግዚአብሔርን ቸርነትና የንስሐን ፍጹምነት የሚያሳይ ነው።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ቅድስት አትናስያ ግብጻዊት ስትሆን የነበረችውም መኑፍ በሚባል አውራጃ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ይህ ዘመን "ዘመነ ከዋክብት" ይባል ነበር። ከቁጥር የበዙ ቅዱሳንም በዘመኑ ነበሩ።

ቅድስት አትናስያም ከክርስቲያን ወላጆች ተወልዳ እንደሚገባ አድጋ ገና በወጣትነቷ ሁለቱም ወላጆቿ ሞቱባት። ነገር ግን ብዙ ሃብት ትተውላታልና ምን እንደምታደርገው ሃሳብ ሆናት። መንፈስ ቅዱስ ግን መልካሙን ሕሊና አደላትና አብርሃማዊ ሥራን ለመሥራት ቆረጠች።

መጀመሪያ አገልጋዮችን አዘጋጀች። እንደየ ወገኑ ለእንግዶችና ለነዳያን ቤትን ሠራች። በጐውን እድል መርጣለችና ለብዙ ዓመታት ለነዳያን በማድላት እንግዶችን በመቀበል ተጠመደች። በዚህ ሥራዋም እግዚአብሔርንም ሰውንም ደስ አሰኘች።

ግብሯ እንዲህ ነው። በሌሊት ጸሎት፣ በመዓልት ግን እንግዶችን መቀበል፣ እግር ማጠብ፣ ማስተናገድ፣ ማስተኛት፣ ስንቅ አሰንቆ መስደድ ነው። በዚህ ግብሯ ከምንም በላይ የወቅቱን ጻድቃን አስደስታለች።

በዚያው ልክ ግን ዲያብሎስ ተቆጥቶ ይከተላት ጀመር። በብዙ ጐዳና አልሳካልህ ቢለውም በክፉ ጐረቤቶቿ አማካኝነት ግን ተሳካለት። የአካባቢዋ ሰዎች ወደ እርሷ ተሰብስበው በብዙ ማታለል ከቅድስና ሕይወቷ ፈቀቅ እንድትል አደረጉ።

እነርሱ መልካም ሥራዋን ያስተዋት በመልክ ቆንጆ ነበረችና ይህንን ተጠቅመው ነው:: "ውበትና ሀብትሽን አታባክኝ።" ብለው ከጐዳና አስወጧት። መጽሐፍ ክፉ ባልንጀርነትን የሚቃወመው ለዚያ ነው። መልካም ክርስቲያን ማለት ባልንጀራውን የሚመርጥ ነው።

የሚገርመው ያን ያህል እንግዳ ተቀብላበት ያላለቀ ገንዘብ አሁን ግን ተመናመነ። ክፉዎቹ ምክራቸውን ቀጠሉ። አካሏን እንድትሸጥ አሳምነው ሴተኛ አዳሪ አደረጓት። በአንዴ ከዚያ የቅድስና ከፍታ ወርዳ አካሏን ለዝሙት የምትሸጥ ሆነች።

ነገሩን የሰሙ ገዳማውያን ሁሉ አዘኑ፤ አለቀሱላት። ይልቁኑ ለእነርሱ የእናት ያህል ደግ ነበረችና ከዲያብሎስ ሴራ ሊታደጓት ቆረጡ። ከመካከላቸውም ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ለዚህ ተግባር መረጡ። እርሱ በአጋንንት ላይ ሥልጣን ያለው ሰው ነውና።

እነርሱ ሱባኤ ይዘውላት አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ ከተማ ሔደ፤ ወደ ቤቷም ደረሰ። ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር። አባ ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ።
"እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት - በሞት ጥላ ሥር እንኳ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም።" እያለ ቀረባት።
(መዝ. ፳፪፥፬)

ፈጠን ብሎ ከጐኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ። አትናስያ ደንግጣ "ምነው?" አለችው። "የአጋንንት ሠራዊት በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው።" አላት። አስከትሎም አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች።

ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን አቃታት። ተስፋም ቆረጠች። ቅዱስ ዮሐንስ ግን "ግዴለሽም፤ ንስሐ ግቢ። ፈጣሪ ይምርሻል።" ብሎ አሳመናት። "እሺ አባቴ" ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ፣ ጫማ ሳትጫማ፣ ሌላ ልብስ ሳትደርብ፣ ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች።

ቤቷን አልዘጋችም። ዘወር ብላ ወደ ኋላም አልተመለከተችም። ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በርሃ ሆነ። ያ በእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት፣ ብርድና ፀሐይ ጐበኘው። ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና "እረፊ" ብሏት ሊጸልይ ፈቀቅ አለ።

መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ መላእክት ከሰማይ የብርሃን ዓምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ። "የማን ነፍስ ትሆን?" ብሎ ወደ አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት። ቅዱሱም "ጌታ ሆይ! ምነው ለንስሐ እንኳ ብታበቃት?" ብሎ አለቀሰ።

ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ፦ "ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው ይቅር ያልኳትና ደስ ይበላችሁ።" አለው። ይህንን የአምላክ ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው። "ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፤ ሰባት ጊዜ ይነሳል።"

<3 ቅድስት ኢዮጰራቅስያ ድንግል <3

ይህች ቅድስት እናት የአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰው ስትሆን ወደ ምናኔ የገባችው ገና በስድስት ዓመቷ ነው። አባቷ ገና በልጅነቷ የሞተባት ኢዮጰራቅስያ ከእናቷ ጋር ለሥራ ወደ ግብጽ ገዳማት ይሔዳሉ። በዚያ ደናግል ጌታችንንና እመቤታችንን ሲያገለግሉ ተመልክታ ተደነቀች።

ምክንያቱን ብትጠይቃቸው ስለ ሰማያዊ ተስፋ ነገሯት። የሰማችው ነገር ቢመስጣት እዚያው ገዳም ውስጥ መኖርን መረጠች። እናት ሥራቸውን ሲጨርሱ "እንሒድ" ብትላትም ያቺ የስድስት ዓመት ብላቴና "እኔ ከእንግዲህ የክርስቶስና የድንግል እናቱ ንብረት ነኝና የትም አልሔድም።" አለቻት።

እናት የሕፃን ልጇን ነገር ሰምታ "ልጄ! አንቺ ያልፈለግሽው ዓለም ለእኔስ ምን ይሰራልኛል?" ብላ እርሷም እንደ ልጇ ገዳሙ ውስጥ ቀረች። ከጥቂት ዓመታት በኋላም እናት ታማ ዐረፈች። ቅድስት ኢዮጰራቅስያም ንጹሕ ተጋድሎዋን ቀጠለች።

ትዕግስት፣ ትሕትና፣ ፍቅር፣ ደግነትና ታዛዥነት በእርሷ ሕይወት ላይ በዝተው መገለጥ ያዙ። እህል የምትቀምሰው በሰባት ቀን አንዴ ብቻ ሆነ። ለጸሎት ስትቆምም እስከ አርባ ቀናት በተመስጦ ትቆይ ነበር። ያቺ ብላቴና ሰይጣንን ከነ ሠራዊቱ አሳፍራዋለችና ታገላት።

በዱላና በመጥረቢያ ሳይቀር ይመታት ነበር። እርሷ ግን ታገሰችው። እጅግ ብዙ ድውያንን ከመፈወስ ደርሳ ድንቅ ተአምራትን ሠራች። በዚህች ቀንም ዐርፋ ለክብረ መንግሥቱ በቃች:: ድንግል ኢዮጰራቅስያ ለገዳሙ ሞገስ ነበረችና በዕረፍቷ ታላቅ ሐዘን ተደረገ።

የቅዱሳት አንስት አምላክ ከንጽሕናቸው፣ ትጋታቸውና ማስተዋላቸው በረከትን ይክፈለን።

ነሐሴ ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት አትናስያ ቡርክት
፪.ቅድስት ኢዮጰራቅስያ ድንግል
፫.ቅዱስ ዴሚና ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
፭.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፮.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
፯.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

"ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው። ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ። ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።"
(፩ጢሞ ፩፥፲፭-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ሐምሌ ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ጳውሎስ መናኒ (ከቤተሰቡ ጋር)
፫.ቅዱስ ሱርያል (እስራልዩ) ሊቀ መላእክት
፬.ቅዱሳን መርቆሬዎስና ኤፍሬም (ሰማዕታት)
፭.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት (ፍልሠቱ)
፮.እናታችን ማርያም ክብራ ኢትዮጵያዊት (የዐፄ ናዖድ ሚስት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
፪.አባ ሣሉሲ ክቡር
፫.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፭.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት

"ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ጌታ ኢየሱስን ተከተሉት። ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ "ምን ትፈልጋላችሁ?" አላቸው። እነርሱም:- "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" አሉት። ትርጓሜው "መምህር ሆይ!"ማለት ነው። "መጥታችሁ እዩ።" አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ። በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ። አሥር ሰዓት ያህል ነበረ። ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ።"
(ዮሐ ፩፥፴፯-፵፩)

"እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ። በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።
"በተነ ለምስኪኖች ሰጠ። ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል።" ተብሎ እንደ ተጻፈ።"
(፪ቆሮ ፱፥፯-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ <3

አቡነ ገሪማ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሮም ውስጥ ነው። ወላጆቻቸው መስፍንያኖስ እና ሰፍንግያ እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት ነበሩ። ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ።

እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው። ስሙን ይስሐቅ ብለው አሳደጉት። ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ። ለሰባት ዓመታት ሕዝቡን በፍትሕ እያስተዳደረ መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል።

አንድ ቀን ግን ከግብጽ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው። ላኪው አባ ጰንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ ንግሥና ምን ያደርግልሃል? ይልቁኑስ በሰማይ ለዘላለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና!" የሚል ነበር።

ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ። ድንገት ግን ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብጽ አባ ጰንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው።

እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው። ሰውነታቸውን በገድል ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር።

አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው አባ ጰንጠሌዎን አዘኑ። ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ።" አሉ። አባ ይስሐቅ ግን "ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል።" ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (ሁለት መቶ ሜትር) ተጠራርጎ ሸሸ።

ይህንን የተመለከቱት አባ ጰንጠሌዎን "ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)።" አሏቸው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም "አቡነ ገሪማ" ተብለው ቀሩ።

አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም ግሩም ነህ።" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል። ይህም የተደረገው በዚህች ዕለት መስከረም ፴ ቀን ነው።

ጻድቁ ወንጌልንና ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል፦
፩. ስንዴ ጧት ዘርተውት በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር። "በጽባሕ ይዘርዕ ወበሠርክ የአርር" እንዲል።
፪. ጧት የተከሉት ወይን በዘጠኝ ሰዓት ያፈራ ነበር።
፫. አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጠበል ሆኖ ዛሬም አለ።
፬. ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች።
፭. አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን አቁመዋታል።

ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። "ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገ እስከ አሥራ ሁለት ትውልድ እምርልሃለሁ። አንተ ግን ሞትን አትቀምስም።" ብሏቸው ተሰወረ። ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ ብሔረ ሕያዋን አድርሰዋቸዋል።

አምላከ አበው ምሥጢራቸውን አይሰውርብን። ከበረከታቸውም ያድለን።

መስከረም ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፪.አባ ሣሉሲ ክቡር ጻድቅ
፫.ብፁዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
፬.ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስ ሐዋርያት (ለወንጌል የተጠሩበት /ማር. ፩፥፲፱/)
፭.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ
፮.አባ አብሳዲ ዘደብረ ማርያም
፯.አባ አሮን ዘገሊላ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
፪.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት

"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ። ሐሴትንም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና።"
(ማቴ ፭፥፲-፲፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሊቁ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ <3

ቅዱሱ ታላቅ የሃይማኖት ጠበቃ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ (የተወለደባት) ግብጽ ናት። የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን በምግባሩ በትምህርቱ ለምዕመናን ጥቅም ሆኗቸዋል። ቅዱስ እለእስክንድሮስ ገና ልጅ ሳለ ምሥጢረ ክርስትናን ይማር ዘንድ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት ሔዷል።

ቅዱስ ጴጥሮስ የግብጽ አሥራ ሰባተኛ ፓትርያርክና ሊቅ ሲሆን በታሪክ የዘመነ ሰማዕታት መጨረሻ ተብሎ ይታወቃል። ከዚህ ሰማዕት ሥር የሚማሩ ብዙ አርድእት ቢኖሩም ሦስቱ ግን ተጠቃሽ ነበሩ።
፩.ቅዱስ እለእስክንድሮስ (ደጉ)
፪.አኪላስ (ውዳሴ ከንቱ ወዳጅ)
፫.አርዮስ (የቤተ ክርስቲያን ጠላት)

ከእነዚህም አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሲታትር ነበር። አኪላስ ደግሞ ሆዱ ዘመዱ ስለ ምንም የማይጨንቀው ሰው ነበር። ቅዱስ እለእስክንድሮስ ግን በጾምና በጸሎት እየተጋ መምህሩን ቅዱስ ጴጥሮስን ለመተካት (ለመምሰል) ይጥር ነበር።

ወቅቱ ዘመነ ሰማዕታት እንደ መሆኑ ቅዱሱ ከመምህሩ ጋር ብዙ ነገሮችን አሳልፏል። አርዮስ ክዶ ቅዱስ ጴጥሮስ ካወገዘው በኋላ እንደ ባልንጀራ ገስጾ ሊመልሰውም ሞክሮ ነበር። ነገር ግን የአርዮስን ክፋት ከጌታ ዘንድ የተረዳው ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሩን እለእስክንድሮስን ጠርቶ መከረው።
"እኔ ከሞትኩ በኋላ አኪላስ ይተካል። ከአርዮስ ጋር ስለሚወዳጅ በስድስት ወሩ ይቀሠፋል። አንተ ግን ከአርዮስ መርዝ ተጠበቅ።" አለው። ይህንን ካለው በኋላ ወታደሮች የቅዱስ ጴጥሮስን አንገት ቆረጡ። ይህ የተደረገውም እ.ኤ.አ በ፫፻፲፩ ዓ.ም ነው።

ወዲያውም አኪላስ ተሾመ። እንደ ተባለውም ከአርዮስ ጋር ስለተወዳጀ በስድስት ወሩ ተቀሰፈ። በዚያው ዓመትም ቅዱስ እለእስክንድሮስ የእስክንድርያ (ግብጽ) አሥራ ዘጠነኛ ፓትርያርክ (ሊቀ ጳጳሳት) ሆኖ ተሾመ።

ሊቁ ሲሾም መልካም አጋጣሚ የነበረው ያ የመከራ ዘመን ማለፉ ሲሆን በጣም ከባዱ ግን የአርዮስ ተከታዮች ከተገመተው በላይ መብዛታቸው ነው። ቅዱሱ ሊቅ በጵጵስና መንበሩ ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲቆይ ዕንቅልፍም ሆነ ዕረፍት አልነበረውም።

በዚህ እየጾመ፣ እየጸለየ፣ ሥጋውን እየጐሰመ ለፈጣሪው ይገዛል። በዚያ ደግሞ ሕዝቡን ነጋ መሸ ሳይል ያስተምራል። ምዕመናንን ከአርዮስ የኑፋቄ መርዝ ለመታደግ በአፍም በመጣፍም (በደብዳቤ) አስተማረ።

ብርሃን የሆነ ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ አትናቴዎስ እያገዘው አርዮስን ከነአበጋዞቹ አሳፈሩት። ለእያንዳንዷ የኑፋቄ ጥያቄ ተገቢውን መንፈሳዊ ምላሽ ከመስጠቱ ባለፈ አርዮስን ከአንዴም ሁለቴ፣ ሦስቴ በጉባኤ አውግዞታል።

ነገሩ ግን በዚህ መቋጨት ባለመቻሉ ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጉባኤ ኒቅያ እንዲደረግ አዋጅ ነገረ። እ.ኤ.አ በ፫፻፳፭ ዓ.ም (በእኛ በ፫፻፲፰ ዓ.ም) ከመላው ዓለም ለጉዳዩ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ስምንት የሚያህሉ ሰዎች ተሰበሰቡ። ከእነዚህ መካከል ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቅነትን ከቅድስና የደረቡ ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራ ያሳለፉ ነበሩ።

ይህንን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲመራ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ እለእስክንድሮስን መረጠ። ሊቁም አበው ቅዱሳንን አስተባብሮ በሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉትን አርዮስን ተከራክሮ ረታው።

በጉባኤው መጨረሻ አርዮስ "አልመለስም።" በማለቱ እርሱን አውግዘው፣ ጸሎተ ሃይማኖትን ሠርተው፣ ሃያ ቀኖናዎችን አውጥተው፣ መጽሐፈ ቅዳሴ ደርሰው፣ አሥራው መጻሕፍትን ወስነውና ቤተ ክርስቲያንን በዓለት ላይ አጽንተው ተለያይተዋል።
የዚህ ሁሉ ፍሬ አበጋዙ ደግሞ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ነው።

እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን "ወልድ ዋሕድ፣ አምላክ፣ ወልደ አምላክ፣ የባሕርይ አምላክ" መሆኑን መስክሮ ክብርን አግኝቷል። የእምነታችንም መሠረቱ ይሔው ነው። ክርስቶስን "ፈጣሬ ሰማያት ወምድር፣ የባሕርይ አምላክ፣ ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ (ከአባቱ ጋር በመለኮቱ የሚተካከል)" ብለው ካላመኑ እንኳን ድኅነት ክርስትናም አይኖርም።

ከጉባኤ ኒቅያ በኋላ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመልካሙ ጐዳና ሲጋደል ምዕመናንንም ሲያጸና ኑሯል። ዘወትር ወንጌልን በፍቅር ያነብ ነበርና ሲጸልይ የብርሃን ምሰሶ ይወርድለት ነበር።

ስለ ውለታውም ቤተ ክርስቲያን በግብጽ ካበሩ አምስቱ ከዋክብት ሊቃውንት እንደ አንዱ ታከብረዋለች። ቅዱሱ ሊቅ በ፫፻፳፰ ዓ.ም (በእኛ በ፫፻፳ ዓ.ም) በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል።

ቸር አምላከ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂ ተኩላ ይጠብቅልን። ከቅዱሱ ሊቅም በረከትን ይክፈለን።

ነሐሴ ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (ሦስተኛ ቀን)
፪.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስ ዲያቆን
፬.አባ ዘክርስቶስ ዘወሎ (ኢትዮጵያዊ ጻድቅ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
፫.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
፭.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)

"..... ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።"
(ይሁዳ ፩፥፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"እንዘ ይፀውረኪ በሐቂፍ ወይስዕመኪ በአፍ
አመ አፍለሰኪ ወልድ ውስተ የማኑ ለዐሪፍ
ጽጌ ዕፀ ገነት ማርያም ዘትጼንዊ ለአንፍ
እንዘ ይትጓድዑ አክናፈ በክንፍ
ለቀበላኪ ወረዱ አእላፍ"

(ለአፍንጫ መዐዛን የምትሰጪ የገነት ዛፍ ማርያም ሆይ፤ ልጅሽ በክንዱ ዐቅፎ በአፉ እየሳመ በቀኙ ሊያሳርፍሽ ባሳረገሽ ጊዜ፤ አንቺን ለመቀበል ክንፍ ለክንፍ እየተጋጩ እልፍ አእላፋት መላእክት ወረዱ።)
(አባ ጽጌ ድንግል ወአባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በዚችም ዕለት ዳግመኛ የሰማዕታት አለቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥጋው ከፋርስ አገር ወደ አገሩ ልዳ በክብር የፈለሰበት ነው። የሥጋውም ፍልሰት ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የሥጋ ፍልሰት ጋር አንድ ሁኗልና ስለዚህም እርሷን መውደዱ የሚያውቁ ሥዕሉን ከሥዕሏ አጠገብ ይሥላሉ በስሙ ለሚማፀኑ የድኅነት ወደብ ይሆን ዘንድ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በኃያሉ ተጋዳይ በጊዮርጊስም ጸሎት በእኛ ላይ ምሕረት፣ ይቅርታ፣ ቸርነት ይሁን፤ ለዘላለሙ አሜን።

"ሰላም ለጊዮርጊስ ተውላጠ ፃማሁ ወሕማሙ።
እንተ ተለዓለ ሞገሰ ስሙ።
በፍልሰትኪ ድንግል ዘተቶስሐ ፍልሰተ ዐፅሙ።
እንዘ ይብል ሶበ ጸለየ ኀቤሃ ቀዲሙ።
ምስለ ፍልሰትኪ ደምርኒ እሙ።"

(ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የትንሣኤና የዕርገት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ዕርገተ ድንግል ማርያም <3

ይህች ዕለት እጅጉን ታላቅና ክብርት ናት። ምክንያቱም የድንግል ማርያም ሥጋዋ ተነስቶ ዐርጐባታልና። ድንግል እመቤታችን ተነሣች ዐረገች ስንል እንደ እንግዳ ደርሶ እንደ ውኃ ፈሶ ወይም በአጋጣሚ የተደረገ አይደለም። ጥንቱን በአምላክ ልቡና ታስቦ ኋላም ትንቢት ተነግሮለት ነው።
ታሪኩ፣ ነገሩ፣ ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር። ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር።
ዓለም ተፈጥሮ አዳምና ሔዋን ስተው መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው በኃዘን ንስሐ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት) በኋላ ከአንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ።" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው።

ከአዳም አንስቶ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት አበው፣ ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ። መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት። ምሳሌም መሰሉላት። ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት።
"እምርሑቅሰ ርእይዋ ወተአምኅዋ" እንዲል።

የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ
ከአዳም በሴት
ከያሬድ በሄኖክ
ከኖኅ በሴም
ከአብርሃም በይስሐቅ
ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
ከይሁዳ በእሴይ፣ በዳዊት፣ በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች።
ከሌዊ ደግሞ በአሮን፣ አልዓዛር፣ ፊንሐስ፣ ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች።

አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በአምስት ሺህ አራት መቶ ሰማንያ አምስት ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት ኃጢአት ሳያገኛት ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች።
(ኢሳ. ፩፥፱ ፣ መኃ. ፬፥፯)
"ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ። (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ )

ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለሦስት ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች። በቤተ መቅደስም ለአሥራ ሁለት ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት ሕብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች። አሥራ አምስት ዓመት በሞላት ጊዜ ጻድቅ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት።

በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማኅጸንዋ ጸነሰችው። ነደ እሳትን ተሸከመችው፤ ቻለችው። "ጾርኪ ዘኢይትጸወር ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ።
(ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ)

ወልደ እግዚአብሔርን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጸንሳ እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው።
(ኢሳ. ፯፥፲፬)
"ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በናዝሬት ገሊላ ለሁለት ዓመታት ቆዩ።

አርዌ ሄሮድስ "እገድላለሁ" ብሎ በተነሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብና በጥም፣ በላበትና በድካም፣ በዕንባና በኃዘን ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ከገሊላ እስከ ኢትዮጵያ ተሰዳለች። ልጇ ጌታችን አምስት ዓመት ከስድስት ወር ሲሆነው ለእርሷ ለድንግል ደግሞ ሃያ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ።

በናዝሬትም ለሃያ አራት ዓመት ከስድስት ወር ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች ነዳያንን እያሰበች ኑራለች። እርሷ አርባ አምስት ዓመት ልጇ ሠላሳ ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምህርት ተአምራት ጀመረ። ለሦስት ዓመት ከሦስት ወርም ከዋለበት እየዋለች ካደረበትም እያደረች ትምህርቱን ሰማች።

የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች። አንጀቷ በኃዘን ተቃጠለ። በነፍሷም ሰይፍ አለፈ። (ሉቃ. ፪፥፴፭)
ጌታ በተነሣ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሣኤውን አየች። ለአርባ ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች።

ከልጇ ዕርገት በኋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች። በጽርሐ ጽዮን ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ኖረች። በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል ሐዋርያትን ስታጽናና ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች።

ዕድሜዋ ስልሳ አራት ዓመት በደረሰ ጊዜ ጥር ፳፩ ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ። ኢየሩሳሌምን ጨነቃት። አካባቢውም በፈውስ ተሞላ። በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ። እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ ለዘላለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ፣ ክብርና ተአምራት ዐረፈች። ሞቷ ብዙዎችን አስደንቋል።
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ" እንዲል።

ከዚህ በኋላ መላእክት እየዘመሩ ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ።
ይህንን ሊቃውንት፦
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል።

በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው።) እነርሱን ቀጥቶ እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል።
በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች።

ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ ፩ ሱባኤ ጀመሩ። ሁለተኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው። እየዘመሩም በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል።

በሦስተኛው ቀን (ነሐሴ ፲፮) እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ ተነሥታ ዐርጋለች። ትንሣኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ መግነዟን ተቀብሏል። ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ገቡ።

ለሁለት ሳምንታት ቆይተው በዚህች ቀንም ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው። በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ፣ ደስታና ምሥጢርንም አዩ። ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው። የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል።

<3 ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን። አእምሮውን፣ ለብዎውን፣ ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን። <3

<3 ቅዱስ ጊጋር ሶርያዊ <3

ይህ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የሶርያ መስፍን የነበረ ሲሆን ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰምቷል። እመ ብርሃን ለስደት ስትወጣ በመጀመሪያ የሔደችው ወደ ሊባኖስ ተራሮች ነው። መስፍኑ ጊጋር ነበርና እርሱም የአምላክ እናትነቷን አምኖ አክብሮ አስተናግዷታል።

ሄሮድስም ይህንን ሲሰማ ጦር አስከትቶ ወደ ጊጋር ሔደ። መስፍኑ ጊጋር ሄሮድስን እንደማይችለው ሲረዳ ድንግል ማርያምን ወደ ግብጽ ሸሽጐ አሸሻት። ሄሮድስንም ፊት ለፊት ተገናኘው። ከአቅሙ በላይ ስለነበረም በወታደሮች ተማርኮ ወደ ሄሮድስ ቀረበ።

እመቤታችንንና ልጇን "አምጣ" ቢለው "አልናገርም" አለው። በዚህ ምክንያት አካሉን ከብዙ ቆራርጦ ገድሎታል። በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ስለ እመ አምላክ ፍቅር የተሰዋ የመጀመሪያው ሰው ተብሎ ይታወቃል። ጌታም ስለ ሃይማኖቱ፣ ፍቅሩና ሰማዕትነቱ ሦስት አክሊላትን ሰጥቶታል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ነሐሴ ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መስቀለ ክርስቶስ
፪.ጻድቃን ቅዱሳን (አባ ስምዖንና አባ ዮሐንስ)
፫.ቅዱስ ባስሊቆስ (ኃያል ሰማዕት)
፬.ቅዱስ ድምጥያና ደቀ መዛሙርቱ (ሰማዕታት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፮.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

"የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።
.....መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ። የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ። እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን።"
(፩ቆሮ ፩፥፲፰-፳፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ታቦር ወአርሞንዔም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ።"
መዝ ፹፰፥፲፪
እንኳን ለበዓለ ደብረ ታቦር በሰላም አደረሳችሁ!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ክርስቲያናዊ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ <3

ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያህል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም። ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒ እና ከአባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ።
ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ ጊዜ) ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር።

ክርስቲያኖችን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በተደረገው የአርባ ዓመታት ዘመቻ አብያተ መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ። ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ። ሚሊየኖች በግፍ አለቁ።

የዚህን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም። ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ ቀርነ ሃይማኖት የቆመው ብዙ ሥርዓት የተሠራው ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና።

ይህች ዕለት ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ የነገሠባት ናት።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በ፫፻፲፪ ዓ.ም ዓለምን አስጨንቀው ሲገዙ ከነበሩ ነገሥታት አንዱ የሮሙ ቄሣር መክስምያኖስ ነበር። ክርስቲያኖችን ከግዛቱ ያጠፋ ዘንድ ብዙ ጊዜ ሞክሯል።

በሰይጣን ምክር አብያተ ክርስቲያናትን ዘግቷል። መጻሕፍትን አቃጥሏል፤ ምዕመናንንም ጨፍጭፏል። ነገር ግን ሰማዕታት አንዱ ሲሰዋ አንድ ሺህውን እየተካ (በእምነት እየወለደ) ነውና እንኳን ሊጠፉ በየቀኑ ይበዙ ነበር።

ምንም የሚሊየኖችን ደም ቢያፈስም ክርስቲያኖች ከጽናታቸው የሚነቃነቁ አልሆኑም። በዚህም ስለ ተበሳጨ ከክርስቲያኖች አልፎ በአሕዛብም ላይ ግፍን ጀመረ። በዚህ ጊዜ ደግሞ የበራንጥያው ንጉሥ ቁንስጣ ዐርፎ ልጁ ቆስጠንጢኖስ ነግሦ ነበርና የሮም ሰዎች ዝናውን ሰሙ።

በእርሱ መንግሥት ፍርድ አይጓደልም፣ ደሃ አይበደልም፣ ግፍም አይፈጸምም ነበርና ይህንን ያወቁ የሮም ሰዎች መልዕክተኛ ልከው ከአውሬው መክስምያኖስ እንዲያድናቸው ተማጸኑት። እርሱም ነገሩን ሲሰማ አዝኖ ከመከራ ሊታደጋቸውም ወዶ ሠራዊቱን አስከትቶ ተነሳ።

ወደ ጦርነት እየሔደ ካረፈበት ወንዝ ዳር በመንፈቀ መዓልት (ስድስት ሰዓት ላይ) ድንገት ከሰማይ ግሩም ተአምርን ተመለከተ። የብርሃን መስቀል በከዋክብት አጊጦ ሰማይንም ሞልቶ ብርሃኑ ፀሐይን ሲበዘብዛት በላዩ ላይም "ኒኮስጣጣን" የሚል ጽሑፍ ተሥሎበት አየ።

"ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ አንድ ደፋር ክርስቲያን ወታደር (አውስግንዮስ ይባላል። አርጅቶ በመቶ አሥር ዓመቱ ሰማዕት ሆኗል።) ወደ ንጉሡ ቀርቦ "ይሔማ አዳኝ ሕይወት የሆነ መስቀለ ክርስቶስ ነው።" ብሎታል።

ይህንን እያደነቀ ሳለም በሌሊት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ መጥቶ ነገሩን ገለጠለት፤ ምሥጢሩንም ተረጐመለት። "ኒኮስጣጣን ማለት 'በዝየ ትመውዕ ጸረከ - በዚህ መስቀል ጠላትህን ድል ታደርጋለህ።' ማለት ነው።" አለው።

በነጋ ጊዜም ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ በሁሉም የጦር እቃ (በወታደሩ፣ በጦሩ፣ በፈረሱ፣ በጋሻው..... ) ላይ የመስቀል ምልክትን ሠርቶ መክስምያኖስን ገጠመው። በኃይለ መስቀሉም ድል አድርጐ ማረከው። የተረፈው የአሕዛብ ሠራዊትም እሸሻለሁ ሲል ድልድይ ተሰብሮበት ወንዝ ውስጥ ገብቶ አለቀ።

ቅዱሱ ንጉሥም በኃይለ መስቀሉ ሮሜን እጅ አደረጋት።
"ሃይማኖተ ክርስቶስ ነሢኦ ወዘመስቀሉ ትርጓሜ
ቆስጠንጢኖስ ዮም ነግሠ በሮሜ
ዘመክስምያኖስ ዕልው ድኅረ ኀልቀ ዕድሜ።"
እንዲል።

ቅዱሱ ንጉሥ ድል አድርጐ በዚህች ቀን ወደ ሮም ሲገባ ከመከራና ሞት የተረፉ ክርስቲያኖች ዕፀ መስቀሉን ይዘው በዝማሬ ተቀብለውታል። እርሱም በዚህች ቀን በ፫፻፲፪ ዓ.ም በሮም ግዛት ሁሉ ላይ ነግሦ ለሰባት ቀናት በዓለ መስቀልን በድምቀት አክብሯል። በዘመኑ ሁሉም ቅዱስ ሚካኤል አልተለየውምና ወዳጁ ሲባልም ይኖራል።

ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት፣ ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል። በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ ዐርፏል።
"ቆስጠንጢኖስ" ማለት "ሐመልማል" ማለት ነው።

ጌትነት ያለው አምላካችን በይቅርታው ይጐብኘን። ደግ መሪ መልካም አስተዳዳሪን ያድለን። ከቅዱሱ ንጉሥም በረከትን ያሳትፈን።

ነሐሴ ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (ጻድቅ ንጉሥ)
፪.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፫.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ድሜጥሮስ
፭.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፮.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፯.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፰.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

"እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።"
(፩ጢሞ ፪፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ <3

አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ትግራይ ተንቤን (መረታ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቻቸው ያፍቅረነ እግዚእና ጽርሐ ቅድሳት ይባላሉ። አጥምቀው "ዓቢየ እግዚእ" ሲሉ ስም ያወጡላቸው የወቅቱ ጳጳስ ሰላማ መተርጉመ መጻሕፍት ናቸው። ትርጉሙም "በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው" ማለት ነው።

ዓቢየ እግዚእ በሕፃንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ። ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ (ደብረ በንኮል) ሔደው መንኩሰዋል።

በገዳሙ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በኋላ ወደ ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን አግኝተዋል። በጊዜው በአርባ ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር።

ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን አፍርተዋል። ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ። ከትግራይ እስከ ደንቢያ ደግሞ ሃገረ ስብከታቸው ነው።

አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት ሲንቀሳቀሱ ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ። ቀኑ ነሐሴ ፲ ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለሦስት ቀናት ባለመጉደሉ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ። ጻድቁ በአካባቢው የነበሩት ኢ-አማንያን (አሕዛብ) ቢሆኑም ራርተዋልና "አምላከ ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ።

ቅዱስ ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ። ይህን ድንቅ ያዩ ከዘጠኝ መቶ አርባ በላይ አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል። ይህም ዘወትር ነሐሴ ፲ ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው (ጐንደር) ይከበራል።

ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ። ያኔ ጐንደር በቀሃና አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች። ጻድቁ ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር።

በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ፣ እባብና መሠል አራዊት ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት። ይህንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ። በፍጹም ልባቸውም ስለ ሕዝቡ ለመኑ።

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምህ የተማጸኑ፣ በቃል ኪዳንህ ያመኑ፣ በምድር አራዊት አይሠለጥኑባቸውም። በሰማይም እሳትን አያዩም። ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም።" ብሏቸው አርጓል።

ጻድቁም የወንጌል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ ገዳማቸው ተንቤን ተመልሰዋል። ይሔው እኛ ምን ብንከፋ ጻድቁንም ብንረሳቸው እግዚአብሔር ግን ዛሬም በጻድቁ ምልጃ ከተማዋን ጠብቆ ይኖራል። ነገን ደግሞ እርሱ ያውቃል። ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ የታነጸበት ቦታ (ጎንደር ቀበሌ ፱ ኪዳነ ምሕረት) ጻድቁ የጸለዩበት ቦታ ነው። እንኳን በወርኀዊ በዓላቸው (በአሥራ ዘጠኝ) ይቅርና በዓመታዊ በዓላቸው (ግንቦት ፲፱ና ነሐሴ ፲) እንኳ ለንግሥ የሚመጣው ሰው ቁጥር ያስተዛዝባል።

አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑረው፣ ሦስት ሙታንን አስነስተው፣ ብዙ ድውያንን ፈውሰው፣ ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝተው፣ የድኅነት ቃል ኪዳንም ተቀብለው በመቶ አርባ ዓመታቸው ግንቦት ፲፱ ቀን ዐርፈዋል። የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እናስባቸው።

ይህች ዕለት ባሕረ ተከዜን ከፍለው ሕዝቡን ያሻገሩባት አሕዛብንም ያጠመቁባት ናትና በገዳማቸው ጐንደር ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናቸውም ይከበራል። በረከታቸው ይደርብን።

<3 ቅዱስ መጥራ ሰማዕት <3

ቅዱሱ በዘመነ ሰማዕታት በድፍረቱ ይታወቅ ነበር። "ክርስቶስን ካዱ፤ ለጣዖት ስገዱ።" እያሉ ሲያስቸግሯቸው በሌሊት ወደ ቤተ ጣዖቱ ገብቶ የአጵሎንን (የጣዖት ስም ነው።) ቀኝ እጁን ገንጥሎ (ወርቅ ነውና።) ለነዳያን መጽውቶታል። አሕዛብ በዚህ ተበሳጭተው በብዙ ስቃይ ገድለውታል።

<3 ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ ሰማዕት <3

በወጣትነቱ መከራን ሲቀበል አሕዛብ ሊያስቱት ሁለት ዘማ ሴቶችን ላኩበት። እርሱ ግን አስተምሮ ክርስቲያን አደረጋቸው። ለሰማዕትነትም በቁ። በየጊዜው ሲያሰቃዩት ብዙ ተአምራትን ይሠራ ነበርና ከሠላሳ ሺህ በላይ አሕዛብ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተሰይፈዋል።

አምላካችን በወዳጆቹ ምልጃ ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይሠውርልን።
አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ፍቅርና በረከት ያብዛልን።

ነሐሴ ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ዓቢየ እግዚእ ኢትዮጵያዊ (ተአምራትን ያደረጉበት)
፪.ቅዱስ መጥራ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ ሰማዕት
፬.ሠላሳ ሺህ ሰማዕታት (የሐርስጥፎሮስ ማኅበር)
፭.ቅዱሳን ቢካቦስና ዮሐንስ (ሰማዕታት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፭.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፮.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፯.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ

"ኑ የእግዚአብሔርንም ድንቅ ሥራ እዩ። ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው።
ባሕርን የብስ አደረጋት። ወንዙንም በእግር ተሻገሩ። በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል።
በኃይሉ ለዘላለም ይገዛል።"
(መዝ ፷፭፥፭-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለካህኑ ሰማዕት ቅዱስ አልዓዛርና ለቅዱሳን ቤተሰቡ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 ቅዱስ አልዓዛር ካህን <3

ይህ ቅዱስ የብሉይ ኪዳን ሰማዕታት ተብለው ከሚታወቁት ዋነኛው ነው። የነበረበት ዘመንም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን "ዓመተ መቃብያ (ዘመነ ካህናት)" ይባላል።

በወቅቱ ሰሎሜ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ይኖር የነበረው ቅዱስ አልዓዛር በኢየሩሳሌም ተወዳጅ ነበር። ሐረገ ትውልዱ ከአሮን ወገን ነውና በክህነቱ ተግቶ ያገለግል ነበር። በዚያ ላይ ሊቀ ካህንነትን በመመረጡ ሕዝቡን ይሠራ፣ ያስተምርና ያስተዳድር ነበር።

ቅዱስ አልዓዛር ከተባረከች ሚስቱ ሰሎሜ ሰባት ወንዶች ልጆችን አፍርቷል። እነርሱንም በሥርዓት አሳድጐ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጐ ነበር። በዚያው ዘመን በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚኖሩ ሦስት እኩያን (ክፉ) ካህናት ነበሩ።

እነዚሁም ሕዝቡን ከማስቸገር ፈጣሪን ከማሳዘን ቦዝነው አያውቁም ነበር። የክፋታቸው መጨረሻ ግን የገዛ ሃገራቸውን ማጥፋት ሆነ።
ነገሩ እንዲህ ነው፦ ሦስቱም ተመካክረው የአልዓዛርን የሊቀ ካህንነት ቦታ ሊቀሙ ወስነው ወደ እርሱ ሔዱና እንዲህ አሉት።

"ሹመት በተርታ ሥጋ በገበታ" ሲሆን ያምራልና እኛ በተራችን በወንበሩ ላይ እንቀመጥ።"
እርሱ ግን "ሕዝቡን ጠይቃችሁ ተሾሙ።" አላቸው። እነርሱም ሕዝቡን ጠርተው "ሹመት ይገባናል።" ቢሏቸው ሕዝቡ መልሶ "አልዓዛርን የሾመው እግዚአብሔር ነውና እናንተም ከፈጣሪ ጠይቃችሁ ተሾሙ።" አሏቸው።

በዚህ ጊዜ ሦስቱ እኩያን ተቆጡ። ምክንያቱም እግዚአብሔር እንደ ማይሰጣቸው ያውቃሉና። ወዲያው ግን ሦስቱም ከአካባቢው ጠፉ። ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ጨካኙ የግሪክ ንጉሥ አንጥያኮስ ሔዱ።

አንጥያኮስ ማለት "ቀኝ ዓይናችሁን ገብሩልኝ።" የሚል ንጉሥ ነው። እርሱን "ኢየሩሳሌም ባለቤት የላትምና ሒደህ ውረራት።" አሉት። "አጥሩ ጥብቅ ነው። በምን እገባለሁ?" ቢላቸው "እኛ በመላ እናስገባሃለን።" አሉት። እርሱም ሁለት መቶ አርባ ሺህ ሠራዊት አስከትቶ ወረደ።

እነርሱ ቀድመው ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ያስወሩ ጀመር። "እናንተ ሹመት ብትነሱንም እኛ ግን አንጥያኮስን ያህል ንጉሥ በእስራኤል አምላክ አሳምነን መጣን።" እያሉ ይሰብኩ ገቡ። ቅዱስ አልዓዛር "አትስሟቸው። በዚያም ላይ አሕዛብ የተቀደሰውን ምድር መርገጥ የለባቸውም።" ብሎ ነበር።

ነገር ግን አንዳንድ ችኩሎች አይጠፉምና ፈጥነው የከተማዋን በር ከፈቱት። ሠራዊቱን ደብቆ ትንሽ ራሱን የቆመ የመሰለው አንጥያኮስ በምክንያት፣ በክፋትና በመላ ሁሉን ሠራዊቱን አስገባ። የሚገርመው በጊዜው የከተማዋ ሕዝብ አሥራ ሁለት እልፍ (መቶ ሃያ ሺህ) ሲሆን ንጉሡ ያስገባው ሠራዊት ግን ሃያ አራት እልፍ (ሁለት መቶ አርባ ሺህ) ሆኖ ተገኘ።

ወዲያው አንጥያኮስ ሕዝቡን ሰበሰበና አልዓዛርን ለብቻው ጠርቶ ተናገረው። "አንተ አምላክህን እንደምትወድ ሰምቻለሁ። አንተ የበጉን መስዋዕት በልተህ ለሥዕለ ኪሩብ ሰግደህ ሕዝቡን ግን እሪያ (አሳማ) እንዲበላና ለፀሐይ እንዲሰግድ አድርግልኝ።" አለው።

ቅዱስ አልዓዛር መለሰለት፦ "እግዚአብሔር የሾመኝኮ በጐ ሃይማኖትን ላስተምር እንጂ ለክፋት አይደለም። ለሕዝቤ የክፋት አብነት ፈጽሞ አልሆንም።" አለው። ያን ጊዜ ንጉሡ በቅዱሱ ላይ ተቆጣ። "የምልህን ካላደረግህ ብዙ ግፍ ይደርስብሃል።" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የፈለግኸውን አድርግ።" አለው።

በዚያን ጊዜ ንጉሡ የቅዱሱን ሚስትና ሰባቱን ልጆች እንዲያመጡለት አዘዘ። ቅዱሱ እያየ ከፊቱ ላይ ሰባቱንም ልጆቹን በሰይፍ አስመታቸውና ሰባቱም ወደቁ። ለአንድ አባት ይህ የመጨረሻው መራራ ፈተና ነው። አልዓዛር ግን ምን አንጀቱ በኀዘን ቢቃጠልም ከልጆቹ ለእግዚአብሔር አድልቷልና ቻለው ታገሠው።

በዚህ ለውጥ እንዳልመጣ ያየው ንጉሡ ሌላ ፍርድ ተናገረ። ቅዱሱንና ሚስቱን (ሰሎሜን) በፈትል ጠቅልለው በሠም ነከሯቸው። (ጧፍ እንደሚሠራበት መንገድ ማለት ነው።)

አሁንም ግን ከአምልኮታቸው ፈቀቅ ባለማለታቸው ትልቅ ብረት ምጣድ ተጥዶ ሁለቱም ከነነፍሳቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ። ቀጥሎም ሕዝቡን እንዲፈጁ አዋጅ ወጣ። በከተማዋ ከነበረው ሕዝብ አርባ ሺህ ያህሉ ተገደሉ።

አርባ ሺህ ያህሉ ሲማረኩ አርባ ሺህ ያህሉን ደግሞ ይሁዳ የሚባል አርበኛ በር ሰብሮ ይዟቸው ሸሸ። "እንሾማለን፤ እንሸለማለን።" ብለው ሕዝባቸውን ያስፈጁ እነዚያ ካህናትም እግዚአብሔር ፈርዶባቸው እነርሱም ተገደሉ። ቅዱሱ የአልዓዛር ቤተሰብ ግን የክብርን አክሊል አግኝተዋል።

የእስራኤል አምላክ ቸሩ እግዚአብሔር እንዲህ ካለው መከራ በኪነ ጥበቡ ይሰውረን። ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን።

ነሐሴ ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አልዓዛር ካህን (ሰማዕት)
፪.ቅድስት ሰሎሜ ሰማዕት (ሚስቱ)
፫.ሰባቱ ቅዱሳን ሰማዕታት (ልጆቹ)
፬.ቅዱስ አሞን ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፫.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፬.አቡነ ኪሮስ
፭.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

"አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ። የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ።
ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት።
የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ።
የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት።
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ። የሚቀብራቸውም አጡ።"
(መዝ ፸፰፥፩-፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቁጽረታ (ጽንሰታ) ለማርያም <3

ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል።
ስለ ምን ነው ቢሉ፦
ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው። አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ።
"ለጽንሰትኪ በከርሥ እንበለ አበሳ ወርኩስ ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ።"
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው፤ የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው።"
(መጽሐፈ ሰዓታት ፣ ኢሳ. ፲፥፱ ፣ መኃ. ፬)

ይህች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል።
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ(አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም።" በሚል ይናቁ ነበር።

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት - ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ። እነርሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም።

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው። አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች። "እንስሳትና አራዊትን እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች።

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ። ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ። በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ። እርሱ፦ ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ በማኅጸኗ ስትደርስ አየ።
እርሷ ደግሞ፦ የኢያቄም በትር አብቦ አፍርቶ ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች። ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን።" አሉ። ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ።

በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ ፯) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ። "ዓለም የሚድንባት የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ።" ብሏቸው ተሠወራቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች።
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም።" እንዳለ ሊቁ።
(ቅዳሴ ማርያም)

<3 ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት <3

ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ ናት። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በዚህች ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልጶስ ይዟቸው ሔደ። በዚያም ጌታ ከእነርሱ ራቅ ብሎ ተቀምጦ ነበርና የማይሰማቸው መስሏቸው እርስ በእርስ ይከራከሩ ገቡ።

የክርክራቸው መነሻ ደግሞ ጌታችን ነበር። የዋሃን (ገና ምሥጢርን ያልተረዱ) ነበሩና አንዱ ተነስቶ "ኤልያስ ነው።" ሌላኛው "ሙሴ" ሦስተኛው "ኤርምያስ ነው።" በሚል ተከራከሩ። ቅዱስ ጴጥሮስ ለብቻው ቆሞ ነበርና ጠርተው "ሃሳባችንን አስታርቅልን፤ ለአንተስ ማን ይመስልሃል?" አሉት።

አረጋዊው ሐዋርያም ተቆጣቸው። "እናንተ እንደምታስቡት እርሱ ከነቢያት አንዱ ሳይሆን "እግዚአ ነቢያት - የነቢያት ፈጣሪ ነው።" አላቸው። ወዲያውም ጌታ ጠርቷቸው ወደ እርሱ ቀረቡ።

ቸር አምላክ "ለምን ተጠራጠራችሁኝ።" ብሎ መገሰጽ ሲችል እንዳይደነግጡ ጥያቄውን በፈሊጥ አደረገ። "የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?" አላቸው። እነርሱም በልባቸው ያለውን የሌላ አስመስለው ተናገሩ።

ጌታችን "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ጸጥ አሉ። ገና ሃይማኖታቸው አልጸናም ነበርና። በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነስቶ "አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው - አንተ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ ነህ።" አለው።
(ማቴ. ፲፮፥፲፮)

ይህች ቃል የክርስትና ሃይማኖት መሠረት ናትና ጌታችን "አንተ ዓለት (መሠረት) ነህ።" ብሎ የቤተ ክርስቲያንን በዚህ እምነት ላይ መመስረት ተናገረ። ለቅዱስ ጴጥሮስም "መራሑተ መንግሥት - የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ (ሥልጣን)" ተሰጠው።

ሊቀ ሐዋርያትነትንም ደረበ። ዛሬ ለበርካቶቹ የጸነነባቸው ይሔው እምነት ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስን "አምላክ ወልደ አምላክ፣ ወልደ ማርያም፣ አካላዊ ቃል፣ ሥግው ቃል፣ ገባሬ ኩሉ፣ የሁሉ ፈጣሪ"ብለው ካላመኑ እንኳን ጽድቅ ክርስትናም የለም።

<3 አፄ ናዖድ ጻድቅ <3

ሃገራችን ኢትዮጵያ ምስፍና ከክህነት ንግሥናን ከጽድቅ ያጣመሩ ብዙ መሪዎች ነበሯት። ከእነዚህ አንዱ ደግሞ አፄ ናዖድ ናቸው። ጻድቁ ንጉሥ የነገሡት ከ፲፬፻፹፯ ዓ.ም እስከ ፲፬፻፺፱ ዓ.ም ሲሆን ለእመቤታችን በነበራቸው ልዩ ፍቅር ይታወቃሉ። ካህን እንደ ነበሩም ይነገራል።

ዛሬ ሁላችን የምንወዳትን ጸሎት (ሰላም ለኪ፣ እንዘ ንሰግድ ንብለኪ.....)ን የደረሷት እርሳቸው ናቸው። ትልቁን መልክአ ማርያምም ደርሰዋል። ይህ መልክእ ጣዕሙ ልዩ ነው።

የጻድቁ ንጉሥ ሚስት (ማርያም ክብራ)፣ ልጆቻቸው (አፄ ልብነ ድንግልና ቡርክት ሮማነ ወርቅ) እጅግ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩ። ንጉሡ አፄ ናዖድ ከባለሟልነት የተነሳ ድንግል ማርያምን "እመቤቴ ስምንተኛው ሺህ መቼ ይገባል? ጊዜውስ እንዴት ያለ ነው?" አሏት።

እመ ብርሃንም በአካል ተገልጻ የዘመኑንና የሰውን ክፋት ነገረቻቸው። ንጉሡም አዝነው "እመቤቴ! ከዚያ ዘመን አታድርሺኝ።" አሏት። በዚህ ምክንያት የስምንተኛው ሺህ ዘመን መስከረም ፩ በ፲፭፻ ዓ.ም ሊገባ እርሳቸው ነሐሴ ፯ ቀን በ፲፬፻፺፱ ዓ.ም ዐርፈዋል።

ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የድንግል እናቱን ጣዕም፣ ፍቅር፣ የቅዱስ ጴጥሮስን ሃይማኖትና የአፄ ናዖድን በረከት ያሳድርብን።

ነሐሴ ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.በዓለ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ ገብርኤል መበሥር
፬.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፭.አፄ ናዖድ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፮.ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ (ወልደ ያዕቆብ-ልደቱ)
፯.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

"መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው። ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል።
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው።....
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል።"
(መዝ ፹፮፥፩-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አባ አብርሃም፣ ቅዱስ ዮሐንስ እና አባ ፊልጶስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ አብርሃም ክቡር ገዳማዊ <3

ጻድቁ ግብፃዊ ሲሆን በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተነሱ ከዋክብት አንዱ ነው። ክርስቲያን ወላጆቹ በሥርዓት አሳድገው "ሚስት አግባ።" አሉት። እሺ እንዳይላቸው ከልጅነቱ ጀምሮ የተመኘው ምናኔ ሊቀርበት ሆነ። እንቢ እንዳይላቸው ደግሞ ወላጆቹ ያዝናሉና የልቡን በልቡ ይዞ "እሺ" አላቸው።

ሠርግ ተደግሶ፣ ተክሊል ተደርሶ፣ ከአንዲት ክርስቲያን ጋር አጋቡት። በጋብቻው ማግስት ግን ከነ ድንግልናው ጠፍቶ በርሃ ገባ። በዚያም አንዲት በዓት አዘጋጅቶ ፈቃደ ሥጋውን እየቀጣ ፈቃደ ነፍሱን እያለመለመ ለአሥር ዓመታት ተቀመጠ።

በእነዚያ ሁሉ ዘመናት የሞቀ አልለበሰም። የላመ የጣመ ነገር አልበላም። የፀሐይ ብርሃን እንኳ አልተመለከተም። በዚያ ወራትም ወሬ ነጋሪ ወደ በዓቱ መጥቶ "ወላጆችህ ዐረፉ። በቤት ውስጥ ከስድስት ዓመት እኅትህ ከማርያ በቀር ማንም የለምና የወላጆችህን ሃብት ውረስ።" አለው።

አባ አብርሃም የሚያደርገውን ያውቃልና ከበርሃ ወጥቶ ወደ ሃገር ቤት ሔደ። ትንሽ እኅቱን (ስድስት ዓመቷ ነበር።) ለቤተ ዘመድ አደራ ሰጥቶ ሃብት ንብረቱን አንድ ሳያስቀር ለነዳያን በትኖ ወደ በዓቱ ተመለሰ። በዚያም እንዳስለመደ በጾምና ጸሎት ተወስኖ ለአሥር ዓመታት ቆየ።

ተጋድሎ በጀመረ በሃያ ዓመቱ እግዚአብሔር ለሌላ አገልግሎት ጠራው። የግብጽ ሊቀ ጳጳስ አባ አብርሃምን አስመጥቶ ቅስናን ሾመውና "ሒደህ ወንጌልን ስበክ።" አለው። ችግሩ እርሱ የተላከባት ሃገር አንድም ክርስቲያን የሌለባት ከመሆኗ በባሰ እጅግ ጨካኝ ናቸው።

ማንም ደፍሮ በዚያ ሃገር ውስጥ ነገረ እግዚአብሔርን የሚናገር ሰው አልነበረም። አባ አብርሃም ወደ ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው እንደ ልማዳቸው መሬት ላይ ጥለው ደበደቡት፤ አጥንቶቹንም ሰባበሩት። ሞቷል ብለው ከከተማ ውጪም ጣሉት።

እርሱ ግን በፈጣሪው ኃይል ጸንቶ ተነሣ። ማስተማሩ ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን ተረድቷልና ስለ እነርሱ ተግቶ ይጸልይ ጀመር። አሕዛብ ጠዋት ቢመጡ በከተማዋ መሐል ላይ ሲጸልይ አገኙት። ስለ ተናደዱ ድጋሚ አካሉን በዱላ ሰባብረው እየጐተቱ ከከተማ አስወጡት። በዚያም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት።

ነገር ግን ጠዋት ሲመለሱ እዚያችው ቦታ ላይ ሲጸልይ አገኙት። ይህ የሚደረገው ለእነርሱ ድኅነት መሆኑን አልተረዱምና እነርሱ በየቀኑ እየደበደቡና እያሰቃዩት እርሱ ስለ እነርሱ እየጸለየ አሥር ዓመታት አለፉ። ቅዱሳን ተስፋ አይቆርጡምና በመጨረሻው ተሳካለት።

የቅዱሱ የዘመናት ጸሎት ፍሬ አፍርቶ እግዚአብሔር በአሕዛብ ልቡና ያደሩ አጋንንትን አራቀለት። አንድ ቀን ጠዋት የሃገሩ ሕዝብ ሁሉ (ወንዱ፣ ሴቱ፣ ትልቁ፣ ትንሹ) ወደ ጻድቁ መጸለያ መጡ። ለእርሱስ የጠብ መስሎት ነበር። እነርሱ ግን በአንድነት በፊቱ ተንበርክከው ሰገዱ። ይቅር እንዲላቸውም ለመኑት።

ቅዱሱ ይህንን ሲመለከት ሐሴትን አደረገ። ሁሉንም በስመ ሥላሴ አጥምቆ ክርስቲያን አደረጋቸው። አብያተ ክርስቲያናትንም አነጸላቸው። በኋላ ግን በጣም ሲወዱትና ሲያከብሩት ተመልክቷልና ከውዳሴ ከንቱ (ስብሐት ብጡል) መለየት ፈለገ። ፈጣሪንም በቸርነቱ እንዲጠብቃቸው ለምኖ በሌሊት ጠፍቶ ወደ ነበረበት በርሃ ገባ።

እርሱ በበርሃ ሁኖ ስለ ትንሽ እኅቱ ማርያ ያስብ ነበርና አስጠራት። "ምን ትፈልጊያለሽ?" አላት። እርሷም "እንዳንተ መሆን" ስላለችው አስተምሮ ፈትኖ አመነኮሳት። ለጥቂት ዓመታት በሥርዓት ከኖረች በኋላ ግን ችግር ተፈጠረ።

ከአንድ መነኩሴ ጋር በነበራት ያልተገባ ቅርርብ የዝሙት ፍላጐታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በኃጢአት ወደቁ። በዚህ ተስፋ ቆርጠው ሁለቱም ቆባቸውን ጥለው ከተማ ገቡ። ይልቁኑ እርሷ (ማርያ) ሴተኛ አዳሪ ሆነች።

በዚያ ሰሞን ቅዱሱ አብርሃም ራእይን ያያል። ትልቅ ዘንዶ አንዲት ርግብን ሲውጣት መልሶም ሲተፋት አይቶ እኅቱ መሆኗን ተረዳ። ወዲያው ጥሩ ልብስና ፈረስ ተውሶ ተነሣና ወደ ከተማ ገባ። የጦር መኮንን መስሎ እኅቱ ቤት ገባ።

ሸሽታ እንዳታመልጠው ቤቱን ዘጋና ራሱን ገለጠላት። ደንግጣ እንደ በድን ብትሆንም እርሱ አረጋጋት። "እኅቴ! ንስሐ ግቢ፤ አምላክ ይራራልሻል።" አላት። ልቧ ወደ ምክሩ አዘንብሏልና የእኅቱን ነፍስ ማርኮ ወደ ገዳም ተመለሰ።

በዚያ በዓት ሠርቶላት ቀኖናም ሰጥቷት ሔደ። ማርያም ስለ ኃጢአቷ ፈንታ የምትገርም የቅድስና ሰው ሆነች። ያየ ሁሉ እየተደነቀባት ከዓመታት ተጋድሎ በኋላ ዐረፈች። አባ አብርሃም በተረፈ ዘመኑ በንጹሕ ገዳማዊ ሕይወት ተጠምዶ ኑሯል።

በዘመኑ ሁሉ በስቆ በከንፈሩም አልባሌ ነገርን ተናግሮ አያውቅም። ልቡ በፈጣሪው ፍቅር የታሠረ ነበርና ሕማማተ ክርስቶስን እያሰበ እንባው ያለማቋረጥ ይፈስ ነበር። ደግና ቅዱስ ሰው አብርሃም በዚህች ቀን ዐርፎ ተቀብሯል።

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ <3

ይህ ቅዱስ የነበረው በዘመነ ሰማዕታት ቢሆንም እንደ ሰማዕታት ስቃይ አልደረሰበትም። ክርስቲያኖችን እንዲገድሉና አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያቃጥሉ ከተመደቡ ወታደሮች አንዱ ነበረ። ታዲያ እንዲገድላቸው የሚሰጡትን ክርስቲያኖች እየወሰደ ይደብቃቸው ነበር።

የመከራው ዘመን እስኪያልፍ ድረስም ይንከባከባቸው ነበር። ሌሎች ወታደሮች እንዳይነቁበት ሁሌም "ክርስቲያኖችን በጣም እጠላለሁ።" እያለ ያወራ ነበር። እርሱ በሌሊት ሁሌም ለጸሎት ይተጋ ነበር። በእንዲህ ያለ ግብር ኑሮም በዚህች ቀን በሰላም ዐርፏል።

<3 አባ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን <3

ደብረ ቢዘን በቀድሞ የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገር (አሁን ኤርትራ) ውስጥ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው። ገዳሙ እመቤታችን ድንግል ማርያም በስደቷ ያረፈችበት፣ ጌታችን የባረከውና የመረጠው ቦታ ነው። አባ ዮሐንስን፣ አባ ናርዶስንና ሌሎች ከዋክብት አበውን ያፈራ ሲሆን የአባ ፊልጶስን ያሕል ግን አልተገኘም።

ጻድቁ በግል የተጋድሎ ሕይወታቸው፣ ገዳሙን በአበ ምኔትነት በመምራታቸውና በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ምስጉን ነበሩ። እርሳቸው ቅዱስ ሆነው አልበቃቸውምና ብዙ ቅዱሳንን ወልደዋል። ይህች ዕለትም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ናት።

አምላከ ጻድቃን ገዳማትን ከመከራ ይጠብቅልን። ከአባቶቻችን ቅዱሳን ጸጋ በረከትንም ይክፈለን።

ነሐሴ ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ አብርሃም ገዳማዊ
፪.ቅድስት ማርያ እኅቱ
፫.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ
፬.አባ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፭.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
፮.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)

"በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሠር አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።
.....የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።"
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ አባት አባ ስምዖን ዘዓምድና ቅድስት ሶፍያ ቡርክት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት (share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ <3

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ ይህ ቅዱስ ነው። ተወልዶ ያደገው በሶርያ (ንጽቢን) ውስጥ ሲሆን ዘመኑም አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። አባ ስምዖን ዘዓምድ የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የልጅነትና የተማሪ ቤት ባልንጀራ ነው።

ሁለቱንም ያስተማራቸው ደግሞ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን ነው። ቅዱሳኑ አባ ስምዖንና ቅዱስ ኤፍሬም ለአገልግሎት ከተለያዩ በኋላ አንድ ቀን ተገናኙ።
ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያምን
"እመቤቴ" እያለ ደጋግሞ በጉባኤ ሲያመሰግናት በመስማቱ "ወንድሜ! ይህን ምሥጢር ማን አስተማረህ?" አለው።

ቅዱስ ኤፍሬምም "ተገልጾልኝ ነው።" እንዳይል ውዳሴ ከንቱን ፈርቶ "ቅዱስ ያዕቆብ ነው ያስተማረኝ።" ቢለው በአባ ስምዖን ጠያቂነት ወደ መቃብሩ ሔደው ቅዱሱን ከሞት ቀስቅሰውታል። እርሱም የእመቤታችንን ክብርና የቅዱስ ኤፍሬምን ጸጋ መስክሮ ዙሮ ዐርፏል።

በዚህ የተገረመው ቅዱስ ስምዖን ለቅዱስ ኤፍሬም ሰግዶለት እመቤቴን ስንቅ ይዞ ወደ በርሃ ሔደ። ተጋድሎን፣ ጾምና ጸሎትን በእረኝነት ሕይወት (በሰባት ዓመቱ) የጀመረው ቅዱስ ስምዖን በርሃ ከገባ በኋላ በእጅጉ አሳደገው። ቅዱሱ በወገቡ የሚሻክር ገመድ አሥሮ ምግብ ሳይበላ ዕለት ዕለት ያጠብቀው ነበር።

ከጊዜ በኋላ ገመዱ ሆዱን ቆርጦት ወደ ውስጥ ገብቶ ነበርና ሲራመድ በእግሩ ደም ጠብ ጠብ ሲል ይታይ ነበር። ይህንን መመልከት ጭንቅ የሆነባቸው መነኮሳት ለአበ ምኔቱ ተናግረው ቁስሉን አድነውና ገመዱን አውጥተው ከገዳም አባርረውታል።

እርሱ ግን ይህንን የሚያደርገው ሕማማተ ክርስቶስን ለመሳተፍ ነው። ከገዳም ከተባረረ በኋላ ቅዱሱ በበርሃ ውስጥ ወደሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ አራዊት፣ እባብና ጊንጥ ከበውት ይጸልይ ነበር። እግዚአብሔር ግን በራእይ ለገዳሙ አበ ምኔት ተገልጾ "ወዳጄን ስምዖንን ካልመለስከው አልምርህም።" አለው።

በዚህ ምክንያት መነኮሳት በጭንቅ ፈልገው አግኝተው ከእግሩ ወድቀው ይቅርታ ጠይቀውታል። እርሱ ግን ከመነሻውም የሚቀየም ልብ አልነበረውም። ቅዱስ ስምዖን ወደ ገዳሙ ተመልሶ ለዘመናት በተጋድሎ ጸንቶ ቀጠለ።

እግዚአብሔር ግን ቅዱሱን ከገዳሙ ወጥቶ ወደ አንዲት ምሰሶ እንዲሔድ ስላዘዘው አሥራ አምስት ሜትር ያህል ርዝመት ባለው ምሰሶ ላይ ቆመ። ከዚህች ቀን በኋላ ነው እንግዲህ "ስምዖን ዘዓምድ (የምሰሶው አባት)" የተባለው። ቅዱሱ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ያለ ምንም ዕረፍት፣ እንቅልፍና መቀመጥ ቆሞ
ጸልዩዋል።

ቦታዋ ለከተማ ቅርብ በመሆኗ ብዙዎችን ፈውሷል። በእርሱ ስብከት ወደ ሃይማኖት የተመለሱ፣ ንስሐ የገቡ ቁጥር የላቸውም። አንዳንዴ ክፉ ሰዎች መጥተው እርሱን በማየት ብቻ ይለወጡ ነበር። ከቆመባቸው ዘመናት አሥራ ሁለት ዓመታት ያህልን ያሳለፈው በአንድ እግሩ ቆሞ ሌላኛው እግር ቆስሎ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የሰይጣን ዱላ ነበር።

ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ ከእነዚህ የተጋድሎ ዘመናት በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል። የዕረፍቱ ዜናም ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ ክህነት ሁሉን አስደንግጧል። እርሱ ለመንጐቹ ዕረፍት ያልነበረው ታላቅ አባት ነበርና። ሊቃነ ጳጳሳት ገንዘውት መኳንንት ተሸክመውት ሥጋው በክብር ዐርፏል። ብዙ ተአምራትም ተደርገዋል።

<3 ቅድስት ሶፍያ ቡርክት <3

ይህች ቅድስት እናት ኢጣሊያዊት (የአሁኗ ጣልያን አካባቢ) ስትሆን የነበረችው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው። ትውልዷ የነገሥታቱ ዘር ውስጥ እንደ መቆጠሩ እጅግ የተከበረች ሴት ነበረች። ምንም ሥጋዊ ክብሯ እንዲህ ከፍ ያለ ቢሆንም መንፈሳዊነቷ የሚደነቅ ነበር።

ከነገሥታቱ ዘር ካገባችው ባሏም ሦስት ሴቶች ልጆችን አፍርታለች። በሃይማኖት ምክንያት መከራ ሲመጣ ስለ ልጆቿ ስትል ሃገሯን ጥላ ተሰደደች። ስለ ክርስትናም በባዕድ ሃገር መጻተኛ ሆነች። ያም ሆኖ ክፉዎቹ እግር በእግር ተከትለው ደረሱባት።

ቅድስት ሶፍያ ከዚህ በላይ መሸሽ አልፈለገችም። ከልጅነታቸው ለተባረኩ ልጆቿ ገድላተ ሰማዕታትን ታስጠናቸው ነበርና አሁን የነገር መከናወኛ ደርሷል። ልጆቿን ቁጭ አድርጋ አዋየቻቸው።

"ልጆቼ! ክርስቶስን የወደደ ክብሩ በሰማይ እንጂ በምድር አይደለም። ገድላቸውን ያነበባችሁትን ቅዱሳት አንስትን አስቡ።" አለቻቸው። ሦስቱ ሕፃናትም "እናታችን አትጨነቂ። እኛ ለአምላክ ፍቅር ተገዝተናል። ስለ ስሙም ደምን ልንከፍል ቆርጠናል። ብቻ የእርሱ ቸርነት ያንቺም ምርቃን አይለየን እንጂ።" አሏት። ቅድስት ሶፍያ በሰማችው ነገር እጅግ ደስ አላት።

ከዚያ ጉዞ ወደ ምስክርነት አደባባይ አደረጉ። ቅድስቷ እናት ሦስቱንም ሕፃናት በመኮንኑ ፊት አቀረበች። አንድ በአንድ ጠየቃቸው። ሁሉም ግን መልሳቸው የተጠናና ተመሳሳይ ሆነበት። "እኛ የክርስቶስ ነን።" ነበር ያሉት። መኮንኑ በቁጣ ሦስቱንም እያከታተለ አስገደላቸው።

ቅድስት እናት ሶፍያ በእንባ እየታጠበች ልጆቿን
በየተራ ቀበረች። ስለ ሃይማኖቷ ክብሯን፣ ሃገሯን፣ ሃብቷን፣ መንግሥቷን ሰጠች። ከምንም በላይ ግን ልጆቿን ሰጠች። ከዚህ በኋላ ግን በመጨረሻው ወደ ልጆቿ መቃብር ሒዳ በእንባ ለመነች።
"ልጆቼን አይ ዘንድ ናፍቄአለሁና ጌታ ሆይ! ውሰደኝ።" አለች። ከደቂቃዎች በኋላም እዚያው ላይ ዐረፈች። የአካባቢው ሰዎች ደርሰው እርሷንም ከልጆቿ ጋር ቀበሯት።

መድኃኔ ዓለም ከታላቁ አባ ስምዖንና ከቅዱሳት አንስት በረከትን ያድለን። ትዕግስታቸውንም ያሳድርብን።

ነሐሴ ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ
፪.ቅድስት ሶፍያ ቡርክትና ደናግል ልጆቿ

ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
፬.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭.አቡነ ዜና ማርቆስ
፮.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
፯.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)

"ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል። እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል።
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል። በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።
ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ። ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ።"
(መዝ ፺፩፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያምና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 ቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም <3

ቸር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ጸጋ አንዱ ጾም ነው። የሰው ልጅ ከፈጣሪው ክብር እንዲደረግለት ክፋትን መስራት የለበትም። መልካም መሆንም ይጠበቅበታል። ለዚህ ምንጮቹ ደግሞ ጾም፣ ጸሎትና ስግደት ናቸው። ያለ እነዚህ ምግባራት መቼም ወደ ጽድቅ መድረስ አይቻልም።

ይቅርና እኛ ክፉዎቹ የሰማይና የምድር ፈጣሪ የክብር ሁሉ ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደ ጊዜ የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው ጾምን ነው። ስለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰባት አጽዋማትን በጉባዔ ሠርታ በአዋጅ እንዲጾሙ ታደርጋለች። ከእነዚህም አንዱ ጾመ ፍልሠታ ነው።

"ፈለሠ - ሔደ፣ ተጓዘ" እንደ ማለት ሲሆን "ፍልሠታ" ማለት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የዕርገት ጉዞ የሚያዘክር ቃል ነው። እመ ብርሃን በዚህ ዓለም ለስልሳ አራት ዓመታት ኑራ ካረፈች በኋላ ሥጋዋ እንደ እኛ አልፈረሰም።

ለጊዜው በዕጸ ሕይወት ሥር ቆይታ እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነስታ ዐርጋለች። እርሷ በሁሉ ነገሯ ቀዳሚና መሪ ናትና። ጾመ ፍልሠታን የጀመሩት አበው ሐዋርያት ሲሆኑ እንድትጾምም ሥርዓት የሠሩ ራሳቸው ናቸው። ከሰባቱ አጽዋማትም እጅግ ተወዳጅና እየተናፈቀች የምትፈጸም ናት።

ካህናትና ምዕመናንም ጾሟን እንደየአቅማቸው ክብር በሚያሰጥ መንገድ ይፈጽሟታል።
የቻሉ ወደ ገዳማት ሔደው ጥሬ እየቆረጠሙ ውኃ እየተጐነጩ ክብርን ያገኛሉ።
ሌሎቹ ደግሞ ባሉበት ደብር አካባቢ እያደሩ ሌሊት ሰዓታቱን፣ በነግህ ኪዳኑንና ውዳሴ ማርያም ትርጓሜውን በሰርክ ደግሞ ቅዳሴውን ይሳተፋሉ።
የኔ ብጤ ደካማ ደግሞ ጠዋት ማታ ወደ ደጇ እየተመላለሰ "አደራሽን ድንግል" ይላታል።

በእርሷ አምነን አፍረን አናውቅምና ነጋ መሸ ሳንል እንማጸናታለን።

ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን። አእምሮውን፣ ልበለብዎውን፣ ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን።

ጾሙን የፍሬ፣ የትሩፋትና የበረከት ያድርግልን።

<3 ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ <3

እጅግ የተወደዱ፣ ሞገስ የሞላላቸውና ፈጣሪያቸውን በክብር ገንዘው የቀበሩ አባቶች ናቸው።

ቅዱስ ዮሴፍ ዘአርማትያስ በእስራኤል ምድር ተወልዶ ያደገ ኦሪትን የተማረ ባለጠጋ ሰው ነው። የተማረ ደግ ሰው ነውና የክርስቶስን መምጣት በተስፋ ይጠብቅ ነበር። ባገኘውም ጊዜ በአዳኝነቱ (በመሲህነቱ) አምኖ በስውር ተከታዩ ነበር።

ወንጌል እንደሚነግረን ቅዱስ ኒቆዲሞስ ደግሞ የአይሁድ አለቃ፣ መምህር፣ ዳኛና ሃብታም ሰው ነበር። እነዚህ ሁሉ ማነቆዎች ግን እርሱን ከፈጣሪው ሊያስቀሩት አልቻሉም። ሌሊት እየመጣ ከጌታችን እግር ይማር ዘንድም አድሎታል። በመካከልም ከአይሁድ ጋር ብዙ ተጋጭቷል።

ሁለቱ አባቶች መድኃኒታችን ስለ እኛ ሲል ሞቶ ባለበት ሰዓት ላይ በእርሱ የደረሰ ይደርስብናል ሳይሉ በድፍረት ሥጋውን ከጲላጦስ ተካሠው ለመኑ። እንባቸው በፊታቸው እየወረደ ከመስቀል አውርደው በዮሴፍ በፍታና በኒቆዲሞስ ሽቱ ገነዙት።
እንዲህ እያሉ፦
"ሙታንን የምታስነሳ ጌታ አንተ ሞትክን?! ደካሞችን የምታጸና ቸር አንተ ደከምክን?!"
በዚያች ሰዓት ጐልጐታ አካባቢ ዝማሬ መላእክትን እየሰሙ የክብር ባለቤትን ቀብረውታል። ጌታችንም ከተነሣ በኋላ በንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።

"እየሳማችሁ አክብራችሁ እንደ ገነዛችሁኝ እኔም በሰማይ በእንቁ ዙፋን ላይ አስቀምጣችኋለሁ።" ብሏቸዋል። "አነ አብረክሙ ዲበ መንበረ ሶፎር" እንዲል። ጻድቃን አበው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በተረፈ ዘመናቸው ወንጌልን ሰብከው ከአይሁድ መከራን ታግሰው በበጐ ሽምግልና ዐርፈዋል።

<3 ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት <3

ቅዱስ አቦሊ የሰማዕታቱ ቅዱስ ዮስጦስና ቅድስት ታውክልያ ልጅ ሲሆን በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያበራ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ሰማዕት ነው። የሚገርመኝ ሦስቱ የግማሹ ዓለም አስተዳዳሪዎች ነበሩ። ዮስጦስ ንጉሥ፣ ታውክልያ ንግሥት፣ አቦሊ ደግሞ ልዑል ነው።

ነገር ግን ይህንን ክብራቸውን በክርስቶስ ፍቅር ጐን ሚዛን ላይ ቢያኖሩት በጣም ቀሎ ታያቸው። ሦስቱም ከዙፋናቸው ወርደው ወገባቸውንም ታጥቀው ባሮቻቸው በነበሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ብዙ ተንገላቱ። መራራ ሞትንም ታገሱ።

በተለይ ቅዱስ አቦሊ ከአንጾኪያ ወደ ግብጽ (ብስጣ) ይዘው አምጥተው ክርስትናውን እንዲተው ያላደረጉት የለም። በቁሙ ቆዳውን ገፈው በቆዳው አቅማዳ ሰፍተው ያንንም አሸክመው የተገፈፈ አካሉን ጨውና ኮምጣጤ እየቀቡ አዙረውታል።

እርሱ ግን ጌታ በላከለት ድንቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ሁሉን ችሎታል። በዘመኑ ብዙ ተአምራትን የሠራ ሲሆን አንድ ጊዜ ቤት ተንዶ አሥራ ስድስት ሰዎች ቢያልቁ የተገፈፈ ቆዳውን እየጣለባቸው ተነስተዋል። በተአምራቱና በተጋድሎውም ብዙ ሺህ አሕዛብን ለክርስትና ብሎም ለሰማዕትነት አብቅቷል።

እርሱም ከብዙ የመከራ ጊዜያት በኋላ በዚህች ቀን አንገቱን ተከልሏል። ጌታችን "ዜናህን የጻፈውን፣ ያነበበውንና የሰማውን ይቅር እለዋለሁ።" ብሎ ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል።

ፈጣሪ ከጻድቃንና ሰማዕታት በረከትን ያድለን። ወርኀ ነሐሴንም ለበረከት ይቀድስልን።

ነሐሴ ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.በአተ ጾመ ፍልሠታ
፪.አበው ሐዋርያት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
፫.ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት
፬.ታላቁ ቅዱስ ጰላሞን ገዳማዊ
፭.ቅድስት ሐና (የእመ ብርሃን እናት)
፮.ቅድስት ሐና ነቢይት (ወለተ ፋኑኤል)
፯.ደናግል ቅዱሳት (የንግሥት ሶፍያ ልጆች)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፬.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፭.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

"የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ። ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። የጌታ ኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት።"
(ዮሐ ፲፱፥፴፰-፵)

"በጽዮን መለከትን ንፉ። ጾምንም ቀድሱ። ጉባዔውንም አውጁ። ሕዝቡንም አከማቹ። ማኅበሩንም ቀድሱ። ሽማግሌዎችንም ሰብስቡ። ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ። ሙሽራው ከእልፍኙ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ።"
(ኢዩ ፪፥፲፭-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

መሐሪ እግዚአብሔር ኃጢአታችሁ በዛ ሰውነታችሁ ከፋ ሳይል በአባታዊ ርኅራኄው ጠብቆ ይሔው ወርኀ ሐምሌን በሰላም አስፈጸመን። አይመስለንም እንጂ በእነዚህ ሠላሳ ቀናት ሚሊየኖች አንቀላፍተዋል፣ ሚሊየኖች በደዌ ዳኝነት ተይዘዋል፣ በርካቶቹም ከሃይማኖታቸው ወጥተዋል።
ታዲያ እኛ ይህ ሁሉ ያልደረሰብን በጐ ስለሆንን አይደለም። ይልቁኑ ቸርነቱ በእኛ ላይ ስለበዛ ብቻ ነው እንጂ። አሁንም በሰላም ከአዲሱ ዘመን እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል።

በዚህች ዕለት ደግሞ እነዚህን ቅዱሳን እናከብራለን።

<3 ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ <3

ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው። አባቱም ዮና ይባላል። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ዓሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል። እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል።

ከእርሱም እያገለገለ ለስድስት ወራት ተምሯል። በወቅቱ ከወንጌላዊው (ወልደ ዘብዴዎስ) ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው።

ጌታ ከጾም (ከገዳመ ቆረንቶስ) በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል። መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ።

በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ።
(ዮሐ. ፩፥፴፯)
ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት
"ለሐዋርያ እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ - ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ።" ብሏል።
(መልክአ ስዕል)

ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ (ፈጣን) አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል።
(ዮሐ. ፮፥፭)
ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ እግር ሥር ተምሮ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ ምንም ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኳል።

ይህች ቀን ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ የተነጋገረባትና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ ያዳነባት ናት። ቅዱስ እንድርያስ ሠላሳ ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጓል።

ቅዱስ እንድርያስም ፍጡር (እንዲሁ ሰው) መስሎት ለጌታችን ስለ ጌታችን ሰብኮለታል፤ መርቆታልም። መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል።

"ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ
ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ
ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ።" እንዲል።

"ማረኝ?" ብሎታል። ጌታችንም "አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ።" ብሎታል። ቅዱሱ ሐዋርያ ለወንጌል አገልግሎት ተግቶ ያረፈው ታኅሣሥ ፬ ቀን ነው።

<3 ቅዱስ ጳውሎስ መናኒ <3

ይህ ቅዱስ መላ ሕይወቱ ድንቅ ነው። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ሲሆን የተባረከች ሚስትና ሁለት ቡሩካን ልጆች የነበሩት አባት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ የነዳያን አባት፣ እጅግ ባለ ጸጋ፣ ቤተሰቡን የቀደሰና ባለ ሞገስ ሰውም ነው።

ታዲያ ምጽዋት ወዳጅ ነውና ሲመጸውት ሲመጸውት ሃብቱ አለቀ። አሁንም መመጽወቱን አላቆመምና ቤቱ ንብረቱ አልቆ ከነ ቤተሰቡ ነዳያን ሆኑ። እርሱ ግን ያለ ምጽዋት ማደር አይችልምና አንድ ሃሳብ መጣለት። ሚስቱንና ልጆቹን መሸጥ እንዳለበት ወሰነ።

እነርሱ እንደ መሪያቸው ፍጹማን ናቸውና በደስታ ሃሳቡን ተቀበሉት። መጀመሪያ ትልቁ ልጅ ተሸጠ። ገንዘቡ ግን አሁንም በምጽዋት አለቀ። ቀጥሎ ትንሹ ልጅ ተሸጠ። አሁንም በምጽዋት አለቀ። ሦስተኛ ደግ ሚስት ተሸጠችና እርሱም ተመጸወተ።

በመጨረሻ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱንም ሽጦ መጸወተና ይህ ድንቅ ሥራ ተጠናቀቀ። ነገሩ ግራ እንዳያጋባን "ተሸጡ" ስንል ለአሕዛብ ወይም ለሌላ ሰው አይደለም። አራቱም የተሸጡት ለገዳማት ሲሆን ገዥዎቹ አበ ምኔቶቹ ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መትቶ ምጽዋትንም ገዳማዊ ሕይወትንም አትርፏል።

በኋላ ወደ ተሸጠበት ገዳም ገብቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ "ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝን ሁሉ ላንተ መልሼ ይሔው መጥቻለሁ።" ጌታም ከሰማይ መለሰለት "ወዳጄ ሆይ! በአንተ ደስ ብሎኛል። ተቀብዬሃለሁ።" አለው። አራቱም ቅዱሳን በንጹሕ ተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈው የማታልፈውን ርስት ወርሰዋል።

<3 ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት <3

ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም። የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው።

በሦስቱ ሰማያት ካሉት ዘጠኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው። መልአኩ እጅግ ርኅሩኅ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው። ለኖኅ መርከብርን ያሣራው ከጥፋት ውኃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው።

በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው። ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እስራልዩ" ይባላል። "የእስራኤል ረዳት" እንደ ማለት ነው። ዛሬ ደግሞ የሊቀ መልአኩ ቅዳሴ ቤቱ ነው።

<3 ቅዱሳን መርቆሬዎስና ኤፍሬም <3

እነዚህ ወጣቶች በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሲሆን ከተወለዱባት ገሊላ ወደ ግብጽ (ገዳመ አስቄጥስ) በምናኔ መጥተዋል። ለሃያ ዓመታትም በክህነት አገልግሎትና በተጋድሎ ኑረዋል።

አንድ ቀን መናፍቃን (አርዮሳውያን) በወታደር ተከበው መጥተው በገዳሙ እንቀድሳለን አሉ። የራሳቸው መስዋዕት መንበሩ ላይም አኖሩ። ከዚያ ያሉ አበው አዘኑ። ወጣቶቹ መርቆሬዎስና ኤፍሬም ግን ለአምላካቸው ቀኑ።

ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው መናፍቃኑን "በክርስቶስ አምላክነት የማያምን በዚህ መቅደስ ውስጥ አይሰዋም።" ብለው በድፍረት የመናፍቃንን መስዋዕት ወደ ውጪ በተኑት። በዚያች ሰዓት መናፍቃኑ ሁለቱን ቅዱሳን ወደ መሬት ጥለው ደበደቧቸው፤ ረገጧቸው። የቅዱሳኑ አጥንቶችም ተሰባበሩ። በመጨረሻ በስቃዩ ብዛት ሁለቱም በአንድነት ዐረፉ።

የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አምላክ ተረፈ ዘመኑን የንስሐ፣ የፍቅርና የአንድነት ያድርግልን። ከወዳጆቹም በረከትን ያድለን።

Читать полностью…
Subscribe to a channel