gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

አምላከ ቅዱስ ሉቃስ ምሥጢሩን፣ ፍቅሩን፣ ጥበቡን ይግለጽልን። ከሐዋርያው በረከትም ያሳትፈን።

ጥቅምት ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ሲላስ አረጋዊ (የቅዱስ ሉቃስ ረድእ)
፫.ቅዱስ ታኦፊላ
፬.አራት መቶ ሰባ ሰባት ሰማዕታት (የቅዱስ ሉቃስ ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፫.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
፬.አባ ጳውሊ የዋህ
፭.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት

"የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ! ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን በእኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ። እኔ ደግሞ ስለ ተማርከው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ።"
(ሉቃ ፩፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱስ አልዓዛር ሐዋርያና አባ ዮሐንስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 እግዝእትነ ማርያም <3

እመቤታችን ድንግል ማርያም የወልደ እግዚአብሔር እናቱ ናትና ሁሉን ትችላለች። እርሱን "ከሃሊ" (ሁሉን ቻይ) ካልን እርሷን "ከሃሊት" ልንላት ይገባል። ልክ ልጇ ሁሉን ማድረግ ሲችል በትእግስት ዝም እንደሚለው እመ ብርሃንም ስንት ነገር እየተደረገ በእርሷ ላይም አንዳንዶቹ ስንት ነገርን ሲናገሩ እንደማትሰማ ዝም ትላለች።

እኛ ኃጥአን ንስሐ እስክንገባ ድረስም "ልጄ! የዛሬን ታገሣቸው?" እያለች ትለምንልናለች። ቸሩ ልጇም ሊምረን እንጂ ሊያጠፋን አይሻምና "እሺ እናቴ!" እያለ ይኼው በዚህ ሁሉ ክፋታችን እስከ ዛሬ ድረስ አላጠፋንም።
¤ቸር ነው።
¤መሐሪ ነው።
¤ይቅር ባይ ነው።
¤ታጋሽ ነው።
¤ርኅሩኅ ነው።
¤ቂምም የለውም። በንስሐ ካልተመለስን ግን አንድ ቀን መፍረዱ አይቀርምና ወገኖቼ ንስሐ እንግባ። ወደ እርሱም እንቅረብ።

ይህቺ ዕለት ለእመቤታችን እስረኞችን የምትፈታባት ናት። የሰው ልጅ በሦስት ወገን እስረኛ ሊሆን ይችላል።
፩.በሥጋዊው አጥፍቶም ሆነ ሳያጠፋ ሊታሠር ይችላል።
፪.በመንፈሳዊው ግን ሰው በኃጢአት ማሠሪያ የሚታሠረው በጥፋቱ ብቻ ነው።
፫.ሌላኛው ማሠሪያ ደግሞ ማዕሠረ ደዌ (በደዌ ዳኝነት) መታሠር ነው። መታመም የኃጢአተኛነት መገለጫ አይደለም።

ታዲያ በዚህች ዕለት እመ ብርሃን ሦስቱንም ማሠሪያዎች እንደምትፈታ እናምናለን። በእስር ቤትም፣ በኃጢአትም ሆነ በደዌ ማሠሪያ የታሠርን ሁላችን በዚሁ ዕለት እንድትፈታን የአምላክ እናትን እንለምናት።

በሦስቱም ማሠሪያዎች የታሠሩ ወገኖቻችንንም እያሰብን "ይባእ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሐን - የእስረኞች ጩኸት ወደ አንተ ይድረስ።" እያልን ልንጸልይ ይገባል።
(መዝ. ፸፰፥፲፩)
እመ ብርሃንንም እንደ ሊቃውንቱ፦
"እማእሠረ ጌጋይ ፍትሕኒ ወላዲተ ክርስቶስ አምላክ።
እምነ ሙቃሔ ጽኑዕ ወእማዕሠር ድሩክ።
ከመ ፈታሕኪዮ ዮም ለማትያስ ላዕክ።" እንበላት።

<3 ቅዱስ አልዓዛር ሐዋርያ <3

ቅዱስ አልዓዛር በሃገረ ቢታንያ ከእኅቶቹ ማርያምና ማርታ ጋር ይኖር ነበር። ሦስቱም ድንግልናቸውን ጠብቅው ጌታችንን ያገለግሉት ነበርና አልዓዛርን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ማርያምና ማርታን ደግሞ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል።

በወንጌል ጌታችን ይወዳቸው እንደነበር ተገልጧል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወድ የሚያበላልጥ ሆኖ አይደለም። ይልቁኑ በምሥጢር እነርሱ ተወዳጅ የሚያደርጋቸውን ሥራ ይሠሩ እንደነበር ሲነግረን ነው እንጂ።

ቅዱስ መጽሐፍ እንደነገረን ጌታችን በነ አልዓዛር ቤት በእንግድነት ይስተናገድ ነበር። በመጨረሻዋ ምሴተ ሐሙስም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለሐዋርያቱ ያቀበላቸው በእነዚህ ቅዱሳን ቤት ውስጥ ነው።

ቅዱስ አልዓዛር በጽኑዕ ታሞ አርፏል። ቅዱሳት እኅቶቹ ማርያምና ማርታ ከታላቅ ለቅሶ ጋር ዕለቱኑ ቀብረውታል።
(ዮሐ. ፲፩)
ቸር ጌታችን ክርስቶስ ከአራት ቀናት በኋላ ሊያስነሳው ይመጣል።

ለስም አጠራሩ ስግደት፣ ክብር፣ ጌትነት ይድረሰውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛር ባረፈ በአራተኛው ቀን ወደ ቢታንያ ደረሰ። ማርታ ቀድማ ወጥታ ከእንባ ጋር ተቀበለችው።

"አዳም ወዴት ነህ?" ያለ (ዘፍ. ፫፥፲፯) የአዳም ፈጣሪ "አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት?" አለ። ቸርነቱ ባሕርዩ ያራራዋልና ማርያም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አብሮ አለቀሰ።

ከዚያም በባሕርይ ሥልጣኑ "አልዓዛር! አልዓዛር!" ብሎ አልዓዛርን አስነሳው። ይህች ተአምርም በአይሁድ ዘንድ ግርምት ሆነች። ለጌታም የሞት ምክንያት አደረጓት። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ እንዲህ ታስተምራለች።
(ዮሐ. ፲፩፥፩-ፍጻሜው)

ቅዱስ አልዓዛር ጌታችን ካስነሳው በኋላ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ (ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ነውና።) ለአርባ ዓመታት ወንጌልን አስተምሮ በ፸፬ ዓ/ም አካባቢ ቆጵሮስ ውስጥ አርፏል።

ይህቺ ዕለት ለቅዱሱ ሐዋርያ በዓለ ፍልሠቱ ስትሆን ይህ የተደረገውም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ቅዱሱ ያረፈው ቆጵሮስ ውስጥ ነው። ግን ባልታወቀ ጊዜና ምክንያት ወደ ኢየሩሳሌም ሒዷል።

አንድ ቀንም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ኢየሩሳሌም ውስጥ ሲቆፍሩ አንድ ሳጥን አገኙ። በላዩ ላይ ደግሞ "ይህ የጌታ ወዳጅ የአልዓዛር ሥጋ ነው።" የሚል ጽሑፍ አግኝተው ደስ ተሰኝተዋል። በታላቅ ዝማሬና ፍስሐም ከኢየሩሳሌም ወደ ቁስጥንጥንያ አፍልሠውታል።

የጌታችን ቸርነቱ፣ የአልዓዛር በረከቱ ይድረሰን።

<3 አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም <3

እኒህ ጻድቅ ሰው ግብጻዊ ሲሆኑ በሰፊው የሚታወቁት በኢትዮጵያና በኢየሩሳሌም ነበር። ገና በወጣትነት የጀመሩትን የተጋድሎ ሕይወት ገፍተው በበርሃ ሲኖሩ የወቅቱ የግብጽ ሲኖዶስ ከበርሃ ጠርቶ የኢየሩሳሌም ጳጳስ እንዳደረጋቸው ይነገራል።

በቅድስት ሃገርም በንጽሕናና በመንኖ ጥሪት ወንጌልን እየሰበኩ ኑረዋል። አባ ዮሐንስ የነበሩበት ዘመን አሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ ደጉ አፄ ዳዊት ነበሩ።

ንጉሡ የግብጽ ክርስቲያኖችን ደም ለመበቀል (በወቅቱ ከሊፋዎች ያሰቃዩዋቸው ነበር።) እስከ ላይኛው ግብጽ ወርደዋል። በሃገር ውስጥ ያሉ ተንባላት አባሪዎቻቸውንም ቀጥተዋል። በዚህ የተደናገጠው የግብጹ ሡልጣን "አስታርቁኝ" ብሎ ስለ ለመነ። ለእርቅ የተመረጡ አባ ዮሐንስና አባ ሳዊሮስ ዘምሥር ናቸው።

እነዚህ አባቶች በ፲፫፻፺ዎቹ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ አልተመለሱም። ምክንያቱም ደጉ አፄ ዳዊት እጅግ ስለ ወደዷቸው "አትሔዱም" ብለው ስላስቀሯቸው ነው። እንዲያውም ለግማደ መስቀሉ መምጣት ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረጉት አባ ዮሐንስ ሳይሆኑ አይቀሩም። ዛሬ የጻድቁ ዕረፍታቸው ነው።

አምላከ ቅዱሳን ስለ ድንግል እናቱ ብሎ ከኃጢአት ሁሉ ማሠሪያ ይፍታን። የወዳጆቹን በረከትም አያርቅብን።

ጥቅምት ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
፪.ቅዱስ አልዓዛር ሐዋርያ
፫.አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም
፬.ቅዱስ ኢዩኤል ነቢይ
፭.ቅዱስ ማትያስ ረድእ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አበው ጎርጎርዮሳት
፪.አቡነ ምዕመነ ድንግል
፫.አቡነ አምደ ሥላሴ
፬.አባ አሮን ሶርያዊ
፭.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

"ጌታ ኢየሱስም 'ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?' አላት።
....ይህንም ብሎ በታላቅ ድምጽ 'አልዓዛር ሆይ ወደ ውጭ ና።' ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ። ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ጌታ ኢየሱስም 'ፍቱትና ይሂድ ተውት።' አላቸው።"
(ዮሐ ፲፩፥፵-፵፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥቅምት ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ (ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፪.ቅዱስ ዮሐንስ ዘጸይለም
፫.አባ ስምኦን ገዳማዊ
፬.ቅዱሳን በርተሎሜዎስና ሚስቱ (ሰማዕታት)
፭.አበው ኤጲስ ቆጶሳት (ሳምሳጢን ያወገዙ)
፮.ጻድቃን እለ መጥራ (ቅዱስ ይምርሐ ቤተ መቅደስ ውስጥ የምናያቸው አጽማቸው የፈሰሰው ቅዱሳን ናቸው።)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፬.አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

"አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል።
በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል።
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው። የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም።
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና። ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ።
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም። ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ።
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው።"
(መዝ ፳፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ቴዎፍሎስ እና ለሰማዕቱ ቅዱስ ሮማኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሊቅ <3

በምድረ ግብጽ ከተነሡና ለቤተ ክርስቲያን አብዝተው ከደከሙ አባቶች አንዱ አባ ቴዎፍሎስ ነው። የተወለደው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ሲሆን ቴዎፍሎስ (ታኦፊላ) በመባል ይታወቃል። ገና ልጅ እያለ ቴዎዶስዮስ ከሚባል ባልንጀራው ጋር በተመሳሳይ ሌሊት ተመሳሳይ ሕልምን ያያሉ። ሁለቱ ሕፃናት ያዩት እንጨት ሲለቅሙ ነበር። ሕልምን የሚተረጉመው ሰውም ቴዎዶስዮስን "ትነግሣለህ" ሲለው ቴዎፍሎስን "ፓትርያርክ ትሆናለህ።" አለው። ለጊዜው አልመሰላቸውም።

ከዚያም ወደ ትምህርት ቤት ገብተው መጻሕፍትን ተምረው ቴዎዶስዮስ ወደ ንጉሡ ከተማ ቁስጥንጥንያ ሲሔድ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ግን የታላቁ ሊቅ አባ አትናቴዎስ ደቀ መዝሙር ሆነ።
በዚያም ከቅዱሱ እየተማረ እያገለገለ ዘመናት አለፉ። ቅዱስ አትናቴዎስ ካረፈ በኋላም ለሁለት ፓትርያርኮች ረዳት ሆኖ ተመርጧል። በመጨረሻ ግን ሕልም ተርጓሚው ያለው አልቀረምና ቴዎዶስዮስ "ታላቁ" ተብሎ በቁስጥንጥንያ ላይ ሲነገሥ ቅዱስ ቴዎፍሎስም ፓትርያርክ (ሊቀ ጳጳሳት) ተብሎ በመንበረ ማርቆስ ላይ ተቀመጠ።
በ፫፻፹፬ ዓ.ም የእስክንድርያ ሃያ ሦስተኛው ሊቀ ጳጳሳት ከሆነ በኋላ የመጀመሪያ ሥራው በዘመኑ ገነው የነበሩ መናፍቃንን መዋጋት ነበር። ለዚህም ይረዳው ዘንድ የእኅቱ ልጅ የሆነውን
ቅዱስ ቄርሎስን ወስዶ አስተማረው። ሁለቱ አባቶች እየተጋገዙም ቤተ ክርስቲያንን ከአራዊት (መናፍቃን) ጠበቁ። ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናውቀውን ጨምሮ ቅዱሱ በርካታ ድርሰቶችንም ደረሰ።

ቅዱስ ቴዎፍሎስን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት፦
፩.ቅዱሱ በዘመኑ ከመንበረ ጵጵስናው በር ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበርና አንዲት ባለ ጸጋ ሴት መጥታ "አባቴ! ምን ያስተክዝሃል?" ስትል ጠየቀችው። ሊቁም "ልጄ! እዚህ የቆምንበት ቦታ ውስጥ ወርቅ ተቀብሮ ሳለ ነዳያን ጦማቸውን ያድራሉ። አባቴ አትናቴዎስ እንዳዘነ አለፈ። እኔም ያው ማለፌ ነው።" አላት። ባለ ጸጋዋም "አባ አንተ ጸሎት፤ እኔ ጉልበትና ሃብት ሁነን እናውጣው?" አለችው።
"እሺ" ብሏት ሱባኤ ገባና ከመሬት በታች ሦስት ጋን ሙሉ ወርቅ ተገኝቶ ደስ አላቸው። ግን በላያቸው ላይ ተመሣሣይ "ቴዳ፣ ቴዳ፣ ቴዳ" የሚል ጽሑፍ ነበረውና ማን ይፍታው። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወደ እመቤታችን አመልክቶ ምሥጢር ተገለጠለትና ሲተረጉመው ማሕተሞቹ ተፈቱ።
ሲተረጐምም
ቴዳ ፩ "ክርስቶስ" ማለት ሆነ። ይሔም ለነዳያን ተበተነ።
ቴዳ ፪ "ቴዎፍሎስ" ማለት ሆነ። አብያተ ክርስቲያናት ታነጹበት።
ቴዳ ፫ ደግሞ "ቴዎዶስዮስ" ሆነ። "የቄሣርን ለቄሣር" እንዲል ሦስተኛው ጋን የአቡነ ኪሮስ ወንድምና የገብረ ክርስቶስ መርዓዊ አባት ለሆነው ለደጉ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ተላከለት።
ንጉሡ ግን ከወርቁ ጥቂት ለበረከት ወስዶ ለአባ ቴዎፍሎስ መለሰለት። አብያተ ጣዖቶችን እያፈረሰ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያንጽም ሥልጣን ሰጠው። ቅዱስ ቴዎፍሎስም በዚህ ገንዘብ በመቶ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትን እንዳነጸበት ይነገራል። በተለይ ደግሞ የቅዱስ ሩፋኤልን ቤት በዓሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያነጸው እርሱ ነው።
(ድርሳነ ሩፋኤል)
የድንግል ማርያምን ሲያንጽም እመቤታችን ተገልጣለታለች።
የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቁን አጽም አፍልሦ ከነቢዩ ኤልሳዕ ጋር ቤቱን ሲቀድስለትም ተአምራት ተደርገዋል። የሠለስቱ ደቂቅን ቤተ ክርስቲያን አንጾ የቀደሰ ጊዜ ደግሞ ቅዱሳኑ ከሰማይ ወርደውለታል።

፪.ቅዱስ ቴዎፍሎስ እመቤታችንን ይወዳት ነበርና ለስምንት ጊዜ ያህል ተገልጣ አነጋግራዋለች። "ደፋሩ አርበኛ" ስትል ጠርታ ሙሉ ዜና ስደቷንና ሕይወቷን አጽፋዋለች።
(ተአምረ ማርያም)

፫.ሕፃናትን ሲያጠምቅም ከብቃት የተነሳ የብርሃን መስቀል ይወርድለት ነበር። ቅዱስ ቴዎፍሎስ በሊቀ ጵጵስና በቆየባቸው ሃያ ስምንት ዓመታት እንዲህ ተመላልሶ በ፬፻፲፪ ዓ.ም ዐርፎ ቅዱስ ቄርሎስ በመንበሩ ተተክቷል። ነገር ግን አንዳንድ የዘመናችን "ጸሐፊ ነን ባዮች" የመናፍቃንን መጻሕፍት እየገለበጡ ቅዱሱን ይሳደባሉና ብንጠነቀቅ እመክራለሁ።

<3 ቅዱስ ሮማኖስ ሰማዕት <3

ይህ ቅዱስ ሰማዕት ብዙ ጊዜ የሚጠራው "ኃያሉ" እየተባለ ነው። በዘመነ ሰማዕታት ከራሱ አልፎ ብዙ ክርስቲያኖችን በድፍረት ያጸናቸው ነበር። በወቅቱ በምድረ ግብጽ መከራው እጅግ ስለ በዛ ብዙዎቹ አልቀው፣ እኩሉም ተሰደው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ መካዳቸውን ሲሰማ ቅዱሱ ለጸሎት ከተወሰነበት ቦታ ወጥቶ ሕዝቡን ሰብስቦ መከራቸው።
"ወገኖቼ! ልቡናችንን በክርስቶስ ፍቅር ካጸናነው ሞት ቀላልና አስደሳች ነገር ነው።" ብሎም አበረታታቸው። ይህን የሰማ መኮንኑ ግን ተቆጥቶ አስጠራው። በዓየር ላይ ዘቅዝቆም ኢ-ሰብአዊ በሆነ ጭካኔ ደሙ እስኪንጠፈጠፍ ድረስ አሰቃየው። ይህ ሁሉ እየሆነበት ቅዱስ ሮማኖስ ልቡ በአምላኩ ፍቅር ተመስጦ ነበርና አንዳች አልመለሰም። መኮንኑ ግን ገርሞት "እንዴት ይህ ሁሉ እየሆነብህ ዝም አልክ?" ቢለው "የሦስት ዓመት ሕፃን ጥራና ስለ እውነተኛው አምላክ ጠይቀው።" አለው። አንድ ሕፃን አስመጥቶ በአደባባይ ጠየቀው። ሕፃኑም መለሰና "አዕምሮ የጐደለህ መኮንን ሆይ! አስተውል። ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም!" ሲል ገሰጸው። መኮንኑ በቁጣ ሕፃኑን በዓየር ላይ አሰቅሎ አስገረፈው። ሕፃኑ ደሙ ሲፈስ እናቱን "ውኃ አጠጪኝ?" አላት። እርሷ ግን "ልጄ! እኔ ውኃ የለኝም። ወደ ሕይወት ውኃ ክርስቶስ ሒድ።" አለችው።
በዚያን ጊዜ መኮንኑ የሕፃኑን ራስና የቅዱስ ሮማኖስን ምላስ አስቆረጠ። ቅዱሱ ግን መንፈሳዊ ልሳን ተሰጥቶት ፈጣሪውን አመሰገነው። የሚያደርገውን ያጣው መኮንኑም በዚህ ዕለት ቅዱሱን ገድሎታል።

አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን ክብሩን አይንሳን። የአባቶቻችንንም በረከት ያብዛልን።

ጥቅምት ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሊቅ
፪.ቅዱስ ሮማኖስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት
፬.ቅድስት አስማኒትና ሰባቱ ልጆቿ
ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
፪.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
፫.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
፬.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፭.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
"ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን። ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን።"
(ሮሜ ፮፥፭-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት፣ ለቅዱስ ፊልያስ እና ለቅድስት ሐና ነቢይት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት <3

በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው። ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እስራኤላውያን አንዱ ነበር።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ። (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ።) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ገባ። የወቅቱ ታላቅ መምህር ገማልያል ይባል ነበር። ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፭፥፴፫ ላይ ተጠቅሷል።

በትውፊት ትምህርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን፣ ጳውሎስን፣ ናትናኤልን፣ ኒቆዲሞስን.....) አስተምሯል። በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር። በፍጻሜውም አምኗል።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ። ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር።

በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ። ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ። ለስድስት ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ።

ለስድስት ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ። በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምህሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው።

"ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው።" በሚል ላከው። ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ እጅ ነስቶ ተማረ።
(ሉቃ. ፯፥፲፰)
በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ። ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው። አጋንንትም ተገዙለት።
(ሉቃ. ፲፥፲፯)

ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ። ምሥጢር አስተረጐመ። ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል።

በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ጵጵስናን) ተሹሟል። በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት ምሥጢርም የተገለጠለት የለም። በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ።

በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ሰባት ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የስድስቱ ዲያቆናት አለቃ እና የስምንት ሺህው ማኅበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል።

ስምንት ሺህ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው። አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው። መጽሐፍ እንደሚል ግን "መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ማሕደረ እግዚአብሔር" ነውና ለእርሱ ተቻለው።
(ሐዋ. ፮፥፭)

አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ "ሊቀ ዲያቆናት" ሲባል እንደ ዘመኑ ይመስለን ይሆናል። እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው። ዲቁናው ለእርሱ "በራት ላይ ዳረጐት" ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም።

ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ስምንት ሺህውን ማኅበር እየመራ ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት "እጠፋ እጠፋ" ወንጌል ደግሞ "እሰፋ እሰፋ" አለች። በዚህ ጊዜ "ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው።" ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት።

እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው። በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት። ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ልቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት።

ይህች ዕለት ለቅዱስ እስጢፋኖስ በዓለ ሲመቱ ናት። ቅዱሱ መጽሐፍ እንደሚል "ምሉዓ ጸጋ ወሞገስ - ሞገስና ጸጋ የሞላለት" (ሐዋ. ፮፥፭፣ ቅዳሴ ማርያም) ነውና የስድስቱ ዲያቆናት አለቃና የስምንት ሺህው ማኅበር መሪ ሆኖ ተመርጦ እንደሚገባ አገልግሏል። በሰማይ ባለችው መቅደስም የሚያገለግለው በዚሁ ማዕረጉ ነው።

<3 ቅዱስ ፊልያስ ሰማዕት <3

ሰማዕቱ የነበረበት ዘመን ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ዘመነ ሰማዕታት) ሲሆን ቀምስ ለምትባል የግብጽ አውራጃም ጳጳስ ነበር። ቅዱሱ እጅግ ጻድቅ በዚያውም ላይ ክቡርና ተወዳጅ ሰው ነበር። የመከራው ዘመን ሲመጣ በቃሉ ያስተማራቸውን እንደ በጐ እረኝነቱ በተግባር ይገልጠው ዘንድ ወደ መኮንኑ ሔደ።

ሕዝቡ በአንድነት ተሰብስበው ሳለ መኮንኑ ቁልቁልያኖስ ቅዱስ ፊልያስን አራት ጥያቄዎችን ጠየቀው። ምላሾቹ ለእኛ ሕይወትነት ያላቸው ናቸውና እንመልከታቸው።

፩."የእናንተ እግዚአብሔር ምን ዓይነት መስዋዕትን ይሻል?" ቢለው "ልበ ትሑተ፣ ወመንፈሰ የዋሃ፣ ወነገረ ሕልወ፣ ወኩነኔ ጽድቅ፣ ዘከመዝ መስዋዕት ያሠምሮ ለእግዚአብሔር - እግዚአብሔርን ትሑት ልቦና፣ የዋህ ሰብእና፣ የቀና ፍርድና ቁም ነገር ደስ ያሰኘዋል።" ሲል መለሰለት።

፪."የምትወዳቸው ሚስትና ልጆች የሉህም?" ሲለው ደግሞ "እምኩሉ የአቢ ፍቅረ እግዚአብሔር - ከሁሉ የእግዚአብሔር ፍቅር ይበልጣል።" አለው።

፫."ለነፍስህ ትጋደላለህ ወይስ ለሥጋህ?" ቢለው "ለሁለቱም እጋደላለሁ። አምላክ በአንድነት ፈጥሯቸዋልና። በትንሣኤ ዘጉባኤም ይዋሐዳሉና።" ብሎታል።

፬."አምላካችሁ የሠራው ምን በጐ ነገር አለ?" ብሎትም ነበር። ቅዱስ ፊልያስ መልሶ "አስቀድሞ ፍጥረታትን በጥንተ ተፈጥሮ ፈጠረ። በኋላም በሐዲስ ተፈጥሮ ያከብረን ዘንድ ወርዶ ሞተልን፣ ተነሣ፣ ዐረገ።" ቢለው መኮንኑ "እንዴት አምላክ ሞተ ትላለህ!" ብሎ ተቆጣ። ቅዱሱም "አዎ! በለበሰው ሥጋ ስለ እኛ ሙቷል።" ብሎ እቅጩን ነገረው።

ወዲያውም "እስከ አሁን የታገስኩህ በዘመድ የከበርክ ስለሆንክ ነው።" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "ክብሬ ክርስቶስ ነው። መልካምን ካሰብክልኝ ቶሎ ግደለኝ?" አለው። በዚያን ጊዜ የሃገሩ ሰዎች "አትሙትብን! እባክህን ለመኮንኑ ታዘዘው?" ሲሉ ለመኑት።

ቅዱስ ፊልያስ "እናንተ የነፍሴ ጠላቶች ዘወር በሉ ከፊቴ! እኔ ወደ ክርስቶስ ልሔድ እናፍቃለሁና።" ብሎ ገሰጻቸው። መኮንኑም ወስዶ ከብዙ ስቃይ ጋር ገድሎታል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባቶቻችን ቅዱሳን አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትና ለቅዱስ ቢላሞን ሰማዕት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት <3

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም። "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው፣ ልዑክ፣ የተላከ፣ የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው። በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፦
የፍጥረታት ሁሉ ጌታ የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ አድጐ፣ ተጠምቆ፣ ጾሞ፣ ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር።

ከተከተሉት የአምስት ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት መረጠ።
እኒህም
፩.ጴጥሮስ የተባለ ስምኦን
፪.እንድርያስ (ወንድሙ)
፫.ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
፬.ዮሐንስ (ወንድሙ)
፭.ፊልጶስ
፮.በርተሎሜዎስ
፯.ቶማስ
፰.ማቴዎስ
፱.ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
፲.ታዴዎስ (ልብድዮስ)
፲፩.ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና
፲፪.ማትያስ (በይሁዳ የተተካ) ናቸው።
(ማቴ. ፲፥፩)

እነዚህን አሥራ ሁለት አርድእቱን ከጠራ በኋላ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር። ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር።

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በኋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው። ለዓለም እረኞች የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ። እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው።
(ማቴ. ፲፥፲፮፣ ዮሐ. ፲፮፥፴፫)
በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው።
(ማቴ. ፲፱፥፳፰)

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ። "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።"
(ማቴ. ፲፰፥፲፰)
"ይቅር ያላችኋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፤ ያላላችኋቸው ግን አይቀርላቸውም።"
(ዮሐ. ፳፥፳፫)

የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. ፲፮፥፲፱)፣ እረኝነትን (ዮሐ. ፳፩፥፲፭) ተቀበሉ። ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው፣ የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. ፭፥፲፫) አላቸው። ወንድሞቹም ተባሉ።
(ዮሐ. ፯፥፭)
ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው።

ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ። ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሣኤ ተመለከቱ። እጆቹን እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ።

ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓት ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው ጌታ ሊቀ ጵጵስናን ሹሟቸው ዐረገ።

ለአሥር ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው። በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን ብርሃናውያን ሆኑ። ሰባ አንድ ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ ሦስት ሺህ ነፍሳትን ማረኩ።
(ሐዋ. ፪፥፵፩)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እስራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል። ከዚህ በኋላ ግን እንደ ትውፊቱ ዓለምን በእጣ ለአሥራ ሁለት ተካፈሏት።

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው። እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ።

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ፣ ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ። በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ። በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ፣ ለምጻሞችን አነጹ፣ እውራንን አበሩ፣ አንካሶችን አረቱ፣ ጐባጦችን አቀኑ፣ ሙታንንም አስነሱ። እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ።

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ፣ ቆዳቸው ተገፈፈ፣ በምጣድ ተጠበሱ፣ ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ። ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ። ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና፤ ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን። "አባቶቻችን፣ መምህሮቻችን፣ ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን።

<3 ቅዱስ ቢላሞን ሰማዕት <3

በዘመነ ሰማዕታት የነበረው ቅዱስ ቢላሞን በወቅቱ ይታወቅ የነበረው በክርስቲያንነቱ ሳይሆን በፈላስፋነቱ ነበር። እጅግ የተማረ ጥበበኛ ግን ደግሞ ወገኑ ከኢ-አማንያን በመሆኑ ክርስቶስን አያውቀውም ነበር።

እግዚአብሔር ግን እንዲጠፋ አልፈቀደምና አንድ ካህንን ላከለት። ከመቀራረብ የተነሳ ብዙ ስለተነጋገሩ ቢላሞን ወደ ክርስትና እየተሳበ ሔደ። በመጨረሻም ተምሮ በካህኑ እጅ ተጠምቋል። ቀጥሎም ይጾም፣ ይጸልይ፣ ይጋደል ነበር።

በትንሽ ጊዜም ከጸጋ ደርሶ ድውያንን ይፈውስ ገባ። ብዙ አሕዛብን እያስተማረ ከደዌአቸውም እየፈወሰ ወደ ክርስትና መለሳቸው። አንድ ቀን ግን "ዓይነ ሥውር አብርተሃል።" በሚል ተከሶ ሞት ተፈረደበት።

ከመገደሉ በፊትም ጌታችን ከሰማይ ወርዶ "ወዳጄ!" ሲለው ወታደሮች ሰሙ። በዚህ ምክንያት አምነው በዚህች ቀን መቶ ሃምሳ ስምንት ወታደሮች አብረውት ተሰይፈዋል።

አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ቸርነቱን ምሕረቱን ያብዛልን። በምልጃቸው ሃገራችንን ከክፉ ጠብቆ ከበረከታቸው ይክፈለን።

ጥቅምት ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ቢላሞን ሰማዕት
፫.መቶ ሃምሳ ስምንት ሰማዕታት (የቅዱስ ቢላሞን ማኅበር)
፬.ቅዱስ ሲላስ ሐዋርያ
፭.ቅድስት ጾመታ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፫.ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ
፬.ቅድስት እንባ መሪና
፭.ቅድስት ክርስጢና

"በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ 'እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ። እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?' አለው። ጌታ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ 'እውነት እላችኋለሁ! እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።"
(ማቴ ፲፱፥፳፯-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳኑ አቡነ አረጋዊ፣ ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ፣ ቅዱስ ሙሴና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ <3

በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው። ጻድቁ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው "ንጉሥ ይስሐቅ" እና "ቅድስት እድና" ይባላሉ። የተወለዱበት አካባቢም ሮም ነው።
ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው። ወላጆቻቸው "ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ።

አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ። በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ጳኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል። ከመነኮሱ ከዓመታት በኋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር ሰባት ያህል የቤተ መንግሥት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል።

"የት ልሒድ?" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮጵያን አሳያቸው። ተመልሰውም ለስምንት ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየኋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር።" ብለው ከስምንቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጡ።

በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ። ወደ ሃገራችን የመጡ በአራት መቶ ሰባዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል። በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል።

ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል። በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን (ደብረ ሃሌ ሉያን) አይተው ወደዷት። የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ ስድሳ ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል።

እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል። በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች። ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በኋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው ስድስት ሺህ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል።

ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮጵያ - የኢትዮጵያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል።

ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ። በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው "ንግሥት እድና" ሁናለች።

ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመታቸው በዚህ ቀን በገዳሙ በስተምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል። ጌታም አሥራ አምስት ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል።

<3 ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ <3

በዘመነ ሐዋርያት በዚህ ስም የሚጠሩ አባቶች ሁለት ነበሩ። አንደኛው ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሲቆጠር ዛሬ የምናከብረው ደግሞ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ይቆጠራል። ቅዱስ ፊልጶስ ያደገው የኖረውም በቂሣርያ አካባቢ ሲሆን ባለ ትዳር የልጆች አባት ነው።

ጌታ ሲጠራው እንኳ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። ከጌታ ሕማማት በፊት ተልኮ አስተምሯል። ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ሰባቱ ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር።
(ሐዋ. ፮)
በቅዱስ እስጢፋኖስ መሪነትም ስምንት ሺህውን ማኅበር አገልግሏል።

ቅዱስ እስጢፋኖስ ተገድሎ ስምንት ሺህው ማኅበር ሲበተንም ቅዱስ ፊልጶስ አራቱን ልጆቹን አስከትሎ ወደ ሰማርያ ወርዷል። በዚያም መሠሪ ስምዖንን ጨምሮ የሃገሪቱን ሰዎች አሳምኖ አጥምቋል።

መቼም ቢሆን እኛ ኢትዮጵያውያን የማንዘነጋው ግን ጃንደረባውን ባኮስን ማጥመቁን እና ለሃገራችን የወንጌልን ብርሃን መላኩን ነው። ጃንደረባው ቅዱስ ባኮስ ከጉዞ መልስ ትንቢተ ኢሳይያስን (ኢሳ. ፶፫) ሲያነብ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቀርቦ ምሥጢረ ሥጋዌን አስረድቶታል።

ሠረገላውም ቁሞለት ቅዱስ ባኮስን አጥምቆት ተነጥቆ ሔዷል።
(ሐዋ. ፰፥፳፮)
ቅዱስ ፊልጶስ በቀሪ ዘመኑ ከተባረኩ አራት ደናግል ልጆቹ ጋር ሲሰብክ ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል።

<3 ሙሽራው ቅዱስ ሙሴ <3

የዚህ ቅዱስ ወጣት ታሪክ ደስ የሚልም የሚገርምም ነው። በሮም ከተማ በምጽዋት፣ በጾምና በጸሎት ከተቃኙ ሃብታሞች (መስፍንያኖስና አግልያስ) ተወልዶ በሥርዓቱ አድጐ መጻሕፍትን ተምሮ በተክሊል አጋቡት።

በሠርጉ ማግስት ሙሽሪትን ቢያያት በጣም ታምራለች። "ይህ ሁሉ ውበትና ምቾት ከንቱ አይደለምን!" ብሎ በሌሊት ጠፍቶ ነዳያንን መስሎ ከሮም ሃገረ ሮሃ (ሶርያ አካባቢ) ሔደ።

በዚያም በፍጹም ምናኔ በሰባት ቀን አንዲት ማዕድ እየበላ በረንዳ ላይ እየተኛና እየለመነ ለዓመታት ኖረ። ሁሌም ቀን የለመነውን ማታ ለነዳያን አካፍሎ እርሱ ሲጸልይ ያድር ነበር። በአካባቢው ክብሩ ሲገለጽበትም የሐዋርያውን የቅዱስ ጳውሎስን በረከት ፍለጋ ወደ ጠርሴስ ሔደ።

ነገር ግን ጥቅል ነፋስ መርከቧን ገፍቶ ሮም አደረሳት። ቅዱስ ሙሴም "የአምላክ ፈቃድ ነው።" ብሎ በወላጆቹ ደጅ ተኝቶ ለአሥራ ሁለት ዓመታት ተጋደለ። ወላጆቹ ፈልገው ስላጡት በበራቸው የወደቀው ነዳይ እርሱ ይሆናል ብለው አልጠረጠሩም።

ከብዙ ተጋድሎም በኋላም ዜና ሕይወቱን ጽፎ በዚህች ቀን በዕለተ እሑድ ዐርፏል። ጌታችንም "መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ ካልተጠራጠረ እምረዋለሁ።" ብሎታል። በዚያም ሕዝቡ፣ ካህናቱና ሊቀ ጳጳሳቱን ጌታ አዝዟቸው አግኝተውታል። ወላጆቹ ማንነቱን በለዩ ጊዜም ታላቅ ለቅሶን አልቅሰዋል። ሥጋውም ብዙ ተአምራትን አድርጓል።

<3 ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ <3

ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ በሃገራቸው ልሳን "አብደል መሲሕ" ይባላል። ለቅዱስ ሙሴና ለሌሎችም ሙሽርነትን ትቶ መመነንን ያስተማረ እርሱ ነው። አባቱ ታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሲሆን እናቱ መርኬዛ ትባላለች። የጻድቃን ትውልድ የተባረከ ነውና (መዝ. ፻፲፩፥፩) ታላቁ አቡነ ኪሮስ አጐቱ ናቸው።

ስለዚህ ቅዱስ ምን እነግራችኋለሁ! ሙሉ ታሪኩ ከቅዱስ ሙሴ ጋር ተመሳሳይ ነውና። ልዩነቱ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ በገዛ ፍቃዱ አካሉ በመቁሰሉ ምክንያት ሰዎች ሊለዩት አልቻሉም ነበር።

በአርማንያ በእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ደጅ ለአሥራ አምስት ዓመታት ሲጋደል ወደ ወላጆቹ ሃገር ቁስጥንጥንያ ተመልሶ ለአሥራ አምስት ዓመታት ተፈትኗል። ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆንም የአባቱ ባሮች በጥፊ ይመቱት፣ ጽሕሙን (ጺሙን) ይነጩት፣ ቆሻሻ ይደፉበትም ነበር።

ለእርሱ ወዳጆቹ ውሾች ነበሩ። በአባቱ ደጅ ለአሥራ አምስት ዓመታት መከራን ከተቀበለ በኋላ "ጌታ ሆይ! የአባቴ አገልጋዮች በእኔ ላይ ያደረጉትን ሁሉ በደል አድርገህ አትቁጠርባቸው።" አለ። በዚህች ቀን ሲያርፍም ጌታችን ሰባቱን ሊቃነ መላእክት ከነ ሠራዊታቸው አስከትሎ ወርዶ በክብር አሳርጐታል። አጠቃላይ የገድል ዓመታቱም ሠላሳ ናቸው።

አምላከ ቅዱሳን ለእነርሱ ካደለው ፍቅራቸው ለእኛም አይንሳን። በረከታቸውንም ያብዛልን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዓለም ሁሉ መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እና ለአባ ዘካርያስ ገዳማዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ <3

ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ፣ ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሐ ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና። አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር "አፈ ወርቅ" መሆን ያስፈልጋል። እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ነገዱ ከሶርያ የተወለደው በ፫፻፵፯ ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ። እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው። ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምህርትና በጥበብ አደገ። ገና በሕፃንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው። በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በአሥራ አምስት ዓመቱ ነበር። በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው።

ቅዱሱ ገና በአሥራ ስድስት ዓመቱ ሃብት፣ ንብረት፣ ውበት፣ ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ። ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ እርሱ መጡ። ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ሥልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት።

ከዚህች ዕለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምሥጢራት ሆነ። ብሉይ ከሐዲስ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራእየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጓሜ ተነተናቸው። በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው። ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት፣ መልዕክታትና ትርጓሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ። በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ ማዕርጉም ዲቁና ነበር።

ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ። በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት። አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም። ከጣዕመ ትምህርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር። ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር። አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል "አፈ ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች። ለዚያም ነው "አፈ ወርቅ" የሚባለው። ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልአከ ሞትን ገስፆ አሥር ዓመት አቁሞታል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም። በርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው። ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር። ምክንያቱም የወቅቱ ንግሥት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ "አልመልስም" በማለቷ መክሮ አወገዛት። እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ ሁለት ጊዜ አጋዘችው። በተሰደደበት ሃገር ፍሬ አፍርቶ፣ አስተምሮና አሳምኖ በ፬፻፯ ዓ/ም አርፏል። ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በስድሳ ዓመቱ አጡት። በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ።

ከዕረፍቱ አስቀድሞ አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ። (ግብዣ አዘጋጀ) በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ አሥራ ሁለቱ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) ከሰማይ በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ።

ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ?" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን። እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና።" አሉት። "እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንዲገለጥልኝ መርቁኝ።" አላቸው። ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ።

በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ጳጳሳቱ፣ ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም። ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ?" ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው።

"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ - የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም።' ማለቱ (ማቴ. ፩፥፳፭) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር።

"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች። ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል። እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር።
'እርሷ ማን ናት? በማኅጸኗ ያለውስ ማን ነው?' እያለ ይጨነቅ ነበር። ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና። አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም።
አሁን ግን ልጇ አምላክ ዘበአማን እርሷም ወላዲተ አምላክ መሆኗን አወቀ ማለት ነው።" እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ በዚያ የነበረች ሥዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች።

ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በሥዕሏ ላይ አደረገ። አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ ....." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት። ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል።

ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው፦
¤ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
¤አፈ በረከት
¤አፈ መዐር (ማር)
¤አፈ ሶከር (ስኳር)
¤አፈ አፈው (ሽቱ)
¤ልሳነ ወርቅ
¤የዓለም ሁሉ መምህር
¤ርዕሰ ሊቃውንት
¤ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
¤ሐዲስ ዳንኤል
¤ሊቀ ጳጳሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
¤መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
¤ጥዑመ ቃል ......

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት፣ ለቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያና ለቅዱስ ድሜጥሮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ <3

ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ "እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ፤ አይጸጸትም።"
(መዝ. ፻፴፩፥፲፩)
አሁን በእግዚአብሔር መጸጸት ኑሮበት አይደለም። ቅዱስ ዳዊት የማያጸጽት ፍጹም ወዳጅ መሆኑን ሲገልጥ ነው እንጂ። ጌታ ቅዱስ ዳዊትን "እንደ ልቤ የሆነ ፈቃዴን የሚፈጽም ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት።" (መዝ. ፹፰፥፲፱) ብሎ ሲናገር ሰምተን እጅግ አደነቅን።

እንደ አምላክ ልብ ሆኖ መገኘት ምን ይረቅ! ምንስ ይደንቅ! ለዚህ አንክሮ ይገባል! ጌታ ይቀጥልና ደግሞ እንዲህ ይላል፦ "ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ።"
(መዝ. ፹፰፥፴፭)
አቤት አባታችን ዳዊት! ክብር፣ የክብር ክብር፣ ውዳሴና ስግደትም ላንተ በጸጋ ይገባል እንላለን።

ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት ሰባት ሃብታት ሲኖሩት
፩.ሃብተ ትንቢት
፪.ሃብተ መንግሥት
፫.ሃብተ ክህነት
፬.ሃብተ በገና (መዝሙር)
፭.ሃብተ ፈውስ
፮.ሃብተ መዊዕ (ድል መንሳት)
፯.ሃብተ ኃይል ተብለው ይታወቃሉ።

በሰባቱ ስሞቹም
፩.ጻድቅ
፪.የዋህ
፫.ንጹሕ
፬.ብእሴ እግዚአብሔር
፭.ነቢየ ጽድቅ
፮.መዘምር እና
፯.ልበ አምላክ ተብሎ ይጠራል።

ይህች ቀን ለእሥራኤል የነገሠባት ቀን ናት። እግዚአብሔር ሳዖልን ከናቀው በኋላ ከእሴይ ልጆች መካከል "እንደ ልቤ የሆነውን ቀብተህ አንግስልኝ።" ቢለው በዚህች ቀን ነቢዩ ሳሙኤል ቤተ ልሔም ገብቷል።

በዚያም ከኤልያብ እስከ አሚናዳብ፣ ሰባቱን የእሴይን ልጆች ቢፈትን አልሆነም። በቅዱስ ሚካኤል ጠቋሚነት ግን ከእረኝነቱ ዳዊት ተጠራ። ገና ከርቀት ሲመጣ የዘይት ቀርኑ ቦግ ብሎ ተከፈተ።

በቅዱስ ዳዊት ራስ ላይም እንደ እሳት ፈላ። በአምላክ ምርጫም በአሥራ ሁለት ዓመቱ ንጉሥ ተባለ። የቅዱሱ ዜና ብዙ ነውና ለታኅሣሥ ፳፫ ይቆየን። በቸር ቢያደርሰን በዚያው ቀን ከክብሩ እንካፈላለን።

<3 ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ <3

ቅዱሱ በቀዳሚ ስሙ "ሌዊ" በቀዳሚ ግብሩ ደግሞ "ቀራጩ" ይባል ነበር። ወንጌል እንደሚል ጌታችን የጠራው ከሚቀርጥበት ቦታ ሲሆን (ማቴ. ፱፥፱) ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ደምሮ (ማቴ. ፲፥፩) ስሙን "ማቴዎስ" ብሎታል። ትርጉሙም "ኅሩይ" (ምርጥ) እንደ ማለት ነው።

ጌታችንን በዘመነ ሥጋዌው በፍጹም ምናኔ ከማገልገሉ ባለፈ ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ የእጁን ተአምራት ተመልክቷል። የቃሉንም ትምህርት ሰምቷል። በጌታ ሕማማት ጊዜ ምንም በፍርሃት ከተበተኑት አንዱ እሱ ቢሆን አመሻሽ ላይ ወደ ማርቆስ እናት ቤት (ጽርሐ ጽዮን) ሒዶ ወንድሞቹን ሐዋርያትን ተቀላቅሏል።

የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቶ ትንሣኤውን ሲገልጥም ቅዱስ ማቴዎስ ነበረ። ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ በጌታ ዕርገት ጊዜ ሊቀ ጵጵስናን ተሹሟል። በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜም ጸጋውንና ሰባ አንድ ልሳናትን ተቀብሎ በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ወንጌልን ሰብኳል።

ሐዋርያት ወንጌልን ለዓለም ለማዳረስ እጣ በተጣጣሉ ጊዜ ለቅዱስ ማቴዎስ ምድረ ፍልስጥኤም ደረሰችው:: ሃገረ ስብከቱን ካዳረሰ በኋላም ወደ ሌሎች ሃገራት ተጉዞ ሰብኳል።

ለምሳሌ በገድለ ሐዋርያት ላይ በኢትዮጵያ፣ በፋርስና በባቢሎን አካባቢ ማስተማሩን ይገልጻል። የሚገርመው ደግሞ ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆን ነገር ሃገራችን ውስጥ መኖሩ ነው።

ወደ አክሱምና አካባቢዋ ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም በሔድንበት ወቅት በጻድቃነ ዴጌ (ዶጌ) ገዳም ውስጥ (አክሱም አካባቢ የሚገኝ የሦስት ሺህ ስውራን ቦታ ነው።) የቅዱስ ማቴዎስን በትረ መስቀል መመልከት ችለናል። አባቶችም ቅዱስ ማቴዎስ በዘመነ ስብከቱ አክሱም አካባቢ መጥቶ እንደ ነበር ነግረውናል።

ቅዱሱ ሐዋርያ በአይሁድ፣ በአሕዛብና በአረሚ መካከል እየተመላለሰ አስተምሮ በርካታ ተአምራትን ሠርቷል። የጣዖት ካህናትንና ነገሥታትን ጨምሮ እልፍ አእላፍ ነፍሳትን ወደ ክርስትና መልሷል።

ስለዚህ ፈንታም እጅግ ብዙ መከራዎች ተፈራርቀውበታል። ጌታችንም በየጊዜው እየተገለጸ ያጽናናው ነበር። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያውን ወንጌል በምድረ ፍልስጥኤም ሲጽፍ ዘመኑም ጌታ ባረገ በስምንተኛው ዓመት (ማለት በ፵፫ ዓ/ም) አካባቢ ነው።

ወንጌሉ ሃያ ስምንት ምዕራፎች ሲኖሩት በጌታ የዘር ሐረግ ጀምሮ የጌታችንን ትምህርቱንና ተአምራቱን በሰፊው ያትታል። በመጨረሻም ከምሴተ ሐሙስ እስከ ትንሣኤ ድረስ አትቶ ይጠናቀቃል።

ቅዱስ ማቴዎስ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በአንድ ነገሩ ይለያል። ከአምስቱ ዓለማት አንዱን (ብሔረ ብጹዓንን) ያስተምር ዘንድ ተመርጧል። ዘወትር እሑድ በደመና እየተነጠቀ ኃጢአት ወደ ሌለበት ዓለም ገብቶ ብጹዓንን ያስተምር ነበር።
"ሰላም ለማቴዎስ በደመና ሰማይ ዘተነጥቀ
ኅሩያነ ይርዓይ ዘብሔረ ብጹዓን ደቂቀ።" እንዲል።

በዚያም ዘወትር ጌታችንን ያየው ነበር። ቅዱስ ማቴዎስ እንዲህ ከተመላለሰ በኋላ በፍጻሜው ለጊዜው ባልለየናት አንዲት ሃገር ውስጥ አረማውያን አስረው አሰቃይተውታል። በዚህች ቀንም ገድለውታል።

<3 ቅዱስ ድሜጥሮስ <3

ቅዱስ ድሜጥሮስ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተወለደ በመንፈሳዊ ለዛ ከአጐቱ ደማስቆስ ጋር ያደገ የዘመኑ ደግ ሰው ነበር። በዘመኑ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ያለቁበት በመሆኑ ቤተሰቦቹ የአጎቱን ልጅ ልዕልተ ወይንን እንዲያገባ ግድ አሉት።

ቅዱስ ድሜጥሮስ የእነርሱን ፈቃድ ለመፈፀም ጋብቻውን በተክሊል ፈፀመ። የፈጣሪውን ፈቃድ ለመፈፀም ደግሞ ከቅድስት እናታችን ልዕልተ ወይን ጋር ተስማምተው ለአርባ ስምንት ዓመታት በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ አንድ ምንጣፍና ልብስ እየተጋሩ በድንግልና ኑረዋል። ቅዱስ ሚካኤልም ስለ ክብራቸው ከመካከላቸው ሆኖ ቀኝ ክንፉን ለእርሱ ግራ ክንፉን ለእርሷ ያለብሳቸው ነበር።

ከአርባ ስምንት ዓመታት በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ የግብጽ አሥራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሹሞ ምሥጢር በዝቶለት ባሕረ ሐሳብን ጽፎ ሠርቷል። ሰይጣን በሰዎች አድሮ ቅዱሱን ሚስት አለው በሚል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከት በመፈጠሩ ቅዱስ ድሜጥሮስ በመልአኩ ትእዛዝ ሕዝቡን ሰብስቦ እሳት አስነድዶ ከቅድስት ልዕልተ ወይን ጋር እሳቱ ውስጥ ገብተው ለረዥም ሰዓት ጸልየዋል።

ሕዝቡም ይህን ተአምር አይተው የቅዱሳኑን ንጽሕና ተረድተው ማረን ብለው በፍቅር ተለያዩ። መጋቢት ፲፪ ቀን ድንግልናው ተገልጧል።

ቅዱስ ድሜጥሮስና እናታችን ልዕልተ ወይን ተረፈ ዘመናቸውን በቅድስና አሳልፈዋል። በተለይ ሊቀ ጳጳሳቱ ድሜጥሮስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል። እነ አርጌንስ (Origen) ና ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ (Clement of Alexandria) የመሰሉ መናፍቃንንም አውግዟል።

ከጣዕመ ስብከቱም የተነሳ አርጅቶ እንኳ ምዕመናን እየተሰበሰቡ ይማሩ ነበር። በአልጋ ተሸክመውትም ይባርካቸው ነበር። ቅዱሱ በመቶ ሰባት ዓመቱ ያረፈው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ በዚህች ቀን ነው።

አምላከ ዳዊት ፍቅሩን፣ አምላከ ማቴዎስ አገልግሎቱን፣ አምላከ ድሜጥሮስ ንጽሕናውን ያሳድርብን። ጸጋ በረከታቸውን ደግሞ ያትረፍርፍልን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሰማዕታት ባኮስ ወሰርጊስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን ባኮስ ወሰርጊስ <3

ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው። ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል። ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው።
ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል። የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው።
"አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ።
ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው።

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ!
በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ። ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም።
እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ።" ብሎናልና።
(ማቴ. ፭፥፵፬)
ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል።

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል። የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና።

እስኪ ለዛሬ ደግሞ በአጭሩ የቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስን ዜና እንካፈል። እነዚህ ቅዱሳን የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ናቸው። ባኮስ እና ሰርጊስ (ሰርግዮስ) ከልጅነት ጀምሮ ባልንጀሮች ናቸው። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ሥር መክስምያኖስና ዲዮቅልጢያኖስ እስከ ነገሡበት ዘመን ድረስ በአንጻሩም ቢሆን ሰላም ነበር።

ታዲያ በዚህ የሰላም ጊዜ ሁለቱ ቅዱሳን ሥራ አልፈቱም። ጾምን፣ ጸሎትንና በጐ ምግባራትን ሁሉ ይከተሉ ነበር። ለመከራ ዘመን ስንቅ የሚሆነን በሰላሙ ዘመን የተያዘ ስንቅ ነውና።

በዚያው አንጻር ደግሞ ሠርቶ መብላት ይገባልና ሥራ ሲፈልጉ መክስምያኖስ ሠራዊት መሰብሰብ ጀመረ። እነርሱም ከሠራዊቱ ዘንድ ተቆጥረው የምድራዊ ንጉሥ ጭፍሮች ሆኑ። በእርግጥ በዘመናችን ለክርስትና አይመቹም ከሚባልላቸው ሥራዎች አንዱ ውትድርና ነው።
ነገር ግን ብዙ ቅዱሳንን ስትመለከቷቸው ሙያቸው ይሔው ነበር። ቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስ ጊዜው የሰላምም ይሁን የጦርነት ይጾማሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይመጸውታሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉም ዘመናት አለፉ።

ከቆይታ በኋላ ግን ሰይጣን ያደረበት ንጉሡ መክስምያኖስ ጣዖት አመለከ። አዋጅም አውጥቶ ክርስቲያኖችን ያሰቃይ፣ ይገድልም ያዘ። ቅዱሳኑ ይህንን ሲሰሙ አዘኑ። ቁጭ ብለውም ተወያዩ። በልባቸው ፍቅረ ክርስቶስ ይነድ ነበርና ወጣትነታቸው፣ መልካቸው፣ ተወዳጅነታቸው ሁሉ ሊያታልላቸው አልቻለም። እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ስለ ሃይማኖት ሊሰው ወሰኑ።

በማግስቱም ንጉሡ ወደ ሾመው የቅርብ አለቃቸው ቀረቡና "የምንነግርህ ነገር አለን።" አሉት። "እሺ" ሲላቸው በወገባቸው ያለውን የክብር መታጠቂያና የክብር ልብሳቸውን በፊቱ ወረወሩለትና "እኛ የክርስቶስ ጭፍሮች ነንና ከዚህ በኋላ ላንተ ለጣዖት አምላኪው አንታዘዝም።" አሉት።

መኮንኑ ነዶታልና አስገረፋቸው፣ አሳሰራቸው። በረሃብና በጥም በብዙ መክፈልተ ኩነኔም አሰቃያቸው። እነርሱ ግን ጽኑዓን ነበሩና አልቻሏቸውም። ጥቅምት ፬ ቀን በሆነ ጊዜ ግን ሁለቱን ለያዩዋቸው። ቅዱስ ባኮስን ለብቻው ወስደው ትልቅ ድንጋይ በአንገቱ ላይ አሠሩበትና ባሕር ውስጥ አሰጠሙት።

ነፍሱም ከሥጋው ስትለይ ባሕር ወደ ዳር አስወጣችው። በአካባቢውም "ባባ" እና "ማማ" የሚባሉ ባሕታውያን ነበሩና እግዚአብሔር እንዲገንዙት አዘዛቸው። ሲሔዱም ቅዱስ ሥጋውን አንበሳና ተኩላ ሲጠብቁት አግኝተው በታላቅ ዝማሬ ገንዘው በራሳቸው ተሸክመው ወስደው በበዓታቸው ውስጥ ቀበሩት።

ቅዱስ ሰርጊስን ደግሞ ለስድስት ቀናት ካሠሩት በኋላ በዚህች ቀን እጁንና እግሩን በእንጨት ላይ ቸንክረው በእንስሳት ጭራ ላይ አስረው ሲጐትቱት ውለዋል። አንገቱን በሰየፉት ጊዜም አንዲት ወጣት ደሙን ተቀብላ በረከትን አግኝታለች። የመከራ ዘመን ካለፈ በኋላም ለቅዱሳኑ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ በዚህች ቀን ተቀድሷል፤ ተአምራትም ታይተዋል።

አምላከ ሰማዕታት ጽንዓት፣ ትእግስታቸውን አሳድሮ ከበረከታቸው ይክፈለን።

ጥቅምት ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስ (ሰማዕታት)
፪.ቅዱስ ዮሐንስ መስተጋድል
፫.አባ አውማንዮስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፭.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፮.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
፯.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን።' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ ፰፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ቶማስ ሐዋርያ፣ እስጢፋኖስ ካልዕና አትናስዮስ ብፁዕ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ <3

ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ከኢትዮጵያ እስከ ሕንድና ባርቶስ በደረሰች ስብከቱ እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ሠርቷል። "እምተአምራቲሁ አሐደ" እንዲሉ አበው ከእነዚህ ዛሬ አንዱን እንመለከታለን።

ቅዱስ ቶማስ ጐና ወደምትባል የሕንድ አውራጃ መግቢያ ፈሊጥ ቢያጣ ጌታ ወርዶ አበኒስ ለሚባል ነጋዴ ባሪያ አድርጐ ይሸጠዋል። በመጀመሪያ በንጉሡ ሠርግ ቤት ውስጥ ተአምራትን አሳይቶ ሕዝቡን ከነ ሙሽሮቹና ንጉሣቸው አሳምኗል።

ቀጥሎ ግን ጎንዶፎር ለሚባል ሌላ ንጉሥ "ቤተ መንግሥት ሥራ።" ተብሎ ይላካል። ሐዋርያውም ንጉሡን "የማንጽበትን ወርቅና ብር ስጠኝ።" ብሎት ይሰጠዋል። ንጉሡ ዘወር ሲል ግን "ወእሁብ ዘንጉሥ ለንጉሥ - የምድራዊውን ንጉሥ ለሰማያዊው ንጉሥ እሰጣለሁ።" እያለ ገንዘቡን ሁሉ ለነዳያን በተነው።

ገንዘቡ ሲያልቅበት "ንጉሥ ሆይ! መሠረቱ ታንጿልና ለግድግዳው ላክልኝ።" ይለዋል። ሲልክለት ይመጸውተዋል:: አሁንም "ንጉሥ ሆይ! ለጣሪያው ላክልኝ።" ይለውና ይመጸውተዋል። መጽሐፍ እንደሚል ምጽዋት ለሐዋርያው ልማዱ ነውና።

በመጨረሻ ግን ንጉሡ ሲመጣ ባዶ መሬት ላይ ነዳያን ገንዘቡን ሲበሉት አገኘ። ተበሳጭቶም ቅዱስ ቶማስን ይገድለው ዘንድ አሠረው። በዚያች ሌሊት ግን የንጉሡ ወንድም ጋዶን ሙቶ ሐዘን በሆነ ጊዜ ሐዋርያው አስነሳው።

ጋዶንም ለቅዱሱ ሰግዶ በሰማይ ለንጉሥ ጐንዶፎር ትልቅ ቤት ታንጾ ማየቱን ተናገረ። ንጉሡና ሠራዊቱም በፊቱ ሰግደው አመኑ፤ አጥምቋቸውም ሔዷል።

<3 ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ <3

በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳን ሊቀ ዲያቆናቱ ቅድሚያውን ሲይዝ ዛሬ የምናከብረው ቅዱስ ደግሞ "ካልዕ እስጢፋኖስ" (ሁለተኛው) ይባላል። ሁለቱም "ቀዳሜ ሰማዕት" ይባላሉ። ዋናው በሐዋርያት ዘመን ቀድሞ እንደተሰዋ ሁሉ ሁለተኛው በዘመነ ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም ቀድሞ ተሰይፏል።

ቅዱሱ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ሲሆን በአንጾኪያ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከነበሩ ልዑላንና የጦር መሪዎችም አንዱ ነበር። በዝምድና ደረጃም የታላቁ ቅዱስ ፋሲለደስ የእኅቱ ልጅ ነው። በቤተ ፋሲለደስ ከማደጉ የተነሳም የእርሱ ልጅ እንደ ሆነ በገድሉ ተጠቅሷል።

ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ ማለት መልክ ከደም ግባት የተባበረለት፣ ጾምና ጸሎትን የሚወድ፣ የነዳያን አጉራሽ፣ ኃያል የጦር ሰውና ተወዳጅ ክርስቲያን ነው። ያ ክፉ አውሬ በዓለም በሚገኙ ምዕመናን ሁሉ ላይ ሞትና ስቃይን ሲያውጅ በአካባቢው የነበረ ይኼው ቅዱስ ነው።

በቦታው ከነበሩ ብዙ ሺህ ሰዎች ንጉሡን ደፍሮ የተናገረው አንድም አልነበረም። ቅዱስ እስጢፋኖስ ግን ለክርስቶስ ቀና። ከሕዝቡ መካከልም እየሮጠ አልፎ በንጉሡ ፊት አዋጅ የሚያነበውን ወታደር ቀማውና በአደባባይ ያችን የክህደት ደብዳቤ ቦጫጭቆ ጣላት።

ንጉሡንም "ሰነፍ" ሲል ገሠጸው። እጅግ የተቆጣው ንጉሡ ግን ቅዱሱን በሰይፍ ሰንዝሮ ከሁለት ከፈለው። አካሉ መሬት ላይ ሲወድቅ ራሱ ግን በዓየር ላይ ሁና ለሦስት ቀናት ትንቢትን ተናገረች። ለዚያ አስጨናቂ የመከራ ዘመንም በር ከፋቹ ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ ሆነ።

<3 ቅዱስ አትናስዮስ ብፁዕ <3

ይህ ቅዱስ አባት ደግሞ ባለ አስደናቂ ታሪክ ነው። ዜና ሕይወቱ ሲሰማ ጣዕመ ነፍስን ያድላል። ተወልዶ ባደገባት ሶርያ በመናኝነቱ የሚታወቀው ቅዱስ አትናስዮስ ሕይወቱ በጽሙና የተሞላ ነበር።
በገዳም ገብቶም በዓት ለይቶ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር ሲያስገዛት ዘመናት አልፈዋል።

በዘመኑ የአንጾኪያ ፓትርያርክ ዐርፎ ነበርና ለመንበሯ የሚገባውን ሰው ፍለጋ በየበርሃው ዞሩ። ነገር ግን ከቅዱሱ አትናስዮስ የተሻለ ሰው አላገኙም። እርሱ መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ለመንጋውም የሚራራ በጐ እረኛ ነውና ይዘውት ወደ ከተማ መጡ።

በሃገራቸው ባሕል መሠረት ሊቀ ጳጳሳት የሚሾመው የሁሉም አሕጉረ ስብከት ጳጳሳት ባሉበት ነውና ጠበቁ። ሁሉ ተገኝቶ በሶርያ የሰልቅ ጳጳስ የነበረው አባ እልመፍርያን ግን ዘገየ። ለሃምሳ ቀናት ጠብቀው አባ አትናስዮስን "ፓትርያርክ ዘአንጾኪያ" ብለው ሹመውት ተለያዩ።

በሃምሳ አንደኛው ቀን አባ እልመፍርያን ሲደርስ በዓለ ሲመቱ መጠናቀቁን ሲነግሩት ተቆጣ። "እኔ በሌለሁበት የተሾመው አይሠራምና አትናስዮስን ፓትርያርክ ብሎ የሚጠራ ሁሉ የተወገዘ ይሁን።" ብሎ ወደ ሰልቅ ተመለሰ። ቅዱስ አትናስዮስ ይህንን ነገር ሲሰማ ፈጽሞ አዘነ።

ከቀድሞውም አስገድደውት እንጂ እርሱ ሹመቱን ፈልጐ አልመጣም። ልክ በዘመኑ እንደምንመለከተው ቅዱሱ መልሶ ማውገዝ ይችላል። ለዚያውም በሥልጣን ይበልጠዋል። ቅዱሱ ግን ለግል ክብሩ ሲል ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ሲከፈሉ ማየትን አልወደደም።

ደቀ መዝሙሩን ጠራውና "ልጄ! እሺ በለኝ ነፍሴ ትመርቅሃለች። እኔ ለአንድ ዓመት መንገድ ስለምወጣ አንተ በእኔ ፈንታ እዘዝ፣ እሠር፣ ፍታ። ሕዝቡ ከጠየቁህ ወደ ገዳም ሔዷል በላቸው።" ብሎት ከመንበረ ጵጵስናው ወጣ። እጅግ የነተበ የበርሃ ልብሱን ለብሶ ለአንድ ቀን በእግሩ ተጉዞ ሰልቅ ውስጥ ደረሰ።

ወደ አባ እልመፍርያን ዘንድ ገብቶም በፊቱ ሰገደ። "አባቴ! ነዳይ ነኝና አስጠጋኝ?" ብሎ ለመነው። አባ እልመፍርያንም ከመነኮሳቱ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት።

ቅዱስ አትናስዮስ ፓትርያርክ ሲሆን ወገቡን ታጥቆ ያገለግል ገባ። ውኃ ይቀዳል፣ ዳቦ ይጋግራል፣ ቤቶችን ይጠርጋል፣ መጸዳጃ ቤቶችን ያጸዳል፣ የመነኮሳቱን እግር ያጥባል። በዚህ ሁሉ ላበቱ እየተንጠፈጠፈ በሰውነቱ ላይ ይወርድ ነበር።

አባቶች ትጋቱንና ትሕትናውን ሲያዩ ለዲቁና አጩት። ጳጳሱም ጠርቶ "ዲቁና ልሹምህ።" ቢለው ፓትርያርኩ ቅዱስ አትናስዮስ አለቀሰ። "ምነው?" ቢለው "አባቴ! በነውር ተይዞብኝ ነው እንጂ ዲቁናስ አለኝ።" አለው። አሁንም ለሰባት ወራት በዲቁና አገልግሎት ቆይቶ ቅስና ተሾም ቢሉት እንደ ቀደመው እያለቀሰ መለሰላቸው።

ልክ በዓመቱ ግን ለአንዲት ሃገረ ስብከት ጳጳስ ያደርጉት ዘንድ በዕለተ እሑድ ተሰበሰቡ። ቅዱስ አትናስዮስ እንዲተውት እያለቀሰ ለመናቸው። "ለሹመቱ ትገባለህ።" ብለው ግድ ሲሉት ግን "ምሥጢር ልንገራችሁ።" ብሎ "ፓትርያርኩ አትናስዮስ ይሏችኋል እኮ እኔ ነኝ።" አላቸው።

የሰማውን ነገር ማመን ያቃተው አባ እልመፍርያን ደንግጦ በግንባሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ እየተንከባለለም አለቀሰ። "ወዬው ለእኔ! ጌታዬን አትናስዮስን እንደ አገልጋይ ላዘዝኩ።" እያለም ተማለለ። በአካባቢው የነበሩ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ምዕመናንም ከቅዱስ አትናስዮስ የትሕትና ሥራ የተነሳ ፈጽመው አደነቁ።

መንበረ ጵጵስና አምጥተው እየዘመሩ ተሸክመውት ዞሩ። ቅዳሴንም ቀድሶ ሥጋውን ደሙን አቀብሏቸው ታላቅ ደስታ ሆነ። በማግስቱም ቅዱሱን ባማረች በቅሎ ላይ አስቀምጠው አባ እልመፍርያን በእግሩ (በራሱ ፈቃድ) እየተጓዘ በታላቅ ዝማሬ አንጾኪያ ደረሱ።

በዚያም ታላቅ የአንድነት በዓል ተከበረ። ታላቁ እረኛ ቅዱስ አትናስዮስ እነሆ በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት ከመከፈል ታደጋት። ቅዱሱ ሲጋደል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል።

ቸሩ አምላክ እንዲህ ለመንጋው የሚራሩ እረኞችን አይንሳን። ከሐዋርያው፣ ከሰማዕቱና ከደጉ ፓትርያርክም ጸጋ በረከትን ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ገዳማዊ ቅዱስ አባ ባውላ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ባውላ መስተጋድል <3

ቅዱሱን የመሰሉ አባቶች በግዕዙ "መስተጋድላን" ይባላሉ። ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው። መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው።
ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ። ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ። የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከሁለቱ አካላት ጋር ነው። በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖታችሁን ካዱ፤ ለጣዖትም ስገዱ።" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው።

በተለይ ሁለተኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል። ታላቁ አባ ባውላ ገዳማዊ ጻድቅ እንደ መሆኑ ትግሉ የነበረው ከአጋንንት ጋር ነው። የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ።
ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ። ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ። ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል።

ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል። ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው። ፍቅረ መስቀሉን የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም።

ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው። ጌታ "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ።" (ማቴ. ፲፮፥፳፬) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን።

ታላቁ አባ ባውላ የተወለደው በላይኛው ግብጽ አካባቢ ሲሆን ዘመኑም አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ከክርስቲያን ወላጆቹ መንፈሳዊ ነገሮችን ተምሮ በወጣትነቱ መንኗል። ያ ዘመን እልፍ አእላፍ ቅዱሳን የነበሩበት ነውና ወደ ጠመው አካባቢ ሔዶ ምናኔን ተምሯል።

ሥርዓተ ገዳምን ማለትም አገልግሎትን፣ ፍቅርን፣ ተጋድሎንና የመሳሰሉትን ከተማረ በኋላም ደቀ መዝሙሩን አባ ሕዝቅኤልን አስከትሎ ለዋናው የተጋድሎ ሕይወት ወደ በርሃ ወጣ። አባ ባውላ ዘወትር በፍቅረ ክርስቶስ ይመሰጥ ነበርና የተጋድሎ ምርጫው ልዩ ሆነ።

አንድ ቀንም እንዲህ ሲል አሰበ "ጌታ ሆይ! አንተ ለእኛ ለኃጥአን ኃፍረተ መስቀልን ታግሰህ ሞትን ከሞትክልን እኛ ደግሞ ስለ ንጹሑ አምላክ ስንል እልፍ ሞትን መታገስ አለብን።"
ይህንን ብሎ ከወትሮው በተለየ መንገድ ሊጋደል ጀመረ። በዚህ እጅግ የጸና ተጋድሎው ምክንያትም ሰባት ጊዜ ሙቶ ሰባት ጊዜ ተነሳ።
፩. እግሩን ከረዥም ዛፍ ላይ አስሮ ወደ ታች ተዘቅዝቆ ይጸልይ ጀመረ። እህልም፣ እንቅልፍም፣ ዕረፍትም አልነበረውምና ደሙ በአፍ በአፍንጫው ፈሶ አለቀ። እንዲህ በሆነ በአርባኛው ቀንም ሞተ። መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ ከሞት አስነሳው።

፪. ጥልቅ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ እንዳስለመደ ይጸልይ ጀመረ። ከባሕሩ ሳይወጣ፣ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋም ሳያጥፍ ለአርባ ቀናት ጸለየ። በዚያው ሳለም ለሁለተኛ ጊዜ ሞተ። ቅዱስ መልአክ መጥቶ ከሞት አስነሳው።

፫. እርሱ በሚኖርበት ጠመው አካባቢ ረዥም ተራራ ነበርና ወደዚያ ወጣ። ከተራራው ጫፍ ሆኖ ወደ ታች ተመለከተ። የተጠራረቡ ድንጋዮች በየመንገዱ ተሰልፈው ነበር። በዚያች ቅጽበት የጌታ ኅማማት ከፊቱ ቢደቀንበት ከላይ ወደ ታች ተወርውሮ ሔደ። በየመንገዱ ያሉት ጥርብ ድንጋዮች ቢቀበሉት አካሉ እየተነተፈና እየተቆራረጠ በየመንገዱ ቀረ፤ በዚህም ሞተ። አሁንም ፈጣሪው ከሞት አስነሳው።

፬. አንድ ቀን ደግሞ (ዕለቱ ዓርብ ነበር።) የጌታን ኅማማት እያሰበ የሚያደርገው ጠፋው። ከቆመበት አካባቢ ትልቅ ዛፍ ነበርና ወደዚያ ወጥቶ ሲመለከት ከመሬት ላይ የተነጠፈ ትልቅ ድንጋይ አየ። ከላይ ወደ ታች ሲወድቅና ድንጋዩ ላይ ሲያርፍ ለሁለት ተከፍሎ ሞተ። አሁንም በፈጣሪ ትዕዛዝ ተነሳ።

፭. በሌላ ቀን ደግሞ በዕለተ ዓርብ ጭንቅላቱን ከእግሩ ጋር አሥሮ ይጸልይ ገባ። ያለ ምንም እህል፣ ውኃና እንቅልፍ ለአርባ ቀናት ቆይቶ ሞተ፤ እንደገናም ተነሳ።

፮. እጅግ ሊመለከቱት እንኳ በሚከብድ የጉድጓድ ውኃ ውስጥ ገብቶ ለአርባ ቀናት እጆቹን ዘርግቶ ቢጸልይ ከጭንቁ ብዛት ነፍሱ ከሥጋው ተለየች።

፯. አንድ ቀንም እንደዚሁ የጌታን ሕማማት እያሰበ ወደ ጽኑ ቆላ ወረደ። በአካባቢው ከአሸዋ በቀር ምንም አልነበረምና ቆሞ ሲጸልይ አሸዋው ውጦ ደፈነውና ለሰባተኛ ጊዜ ሞተ። በዚህ ጊዜ ግን ሊያስነሳው የመጣው እንደ ወትሮው ቅዱስ መልአክ ሳይሆን ራሱ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ ነበር።

ጌታችን አባ ባውላን ከሞተበት አስነስቶ "ወዳጄ ባውላ! ስለ እኔ ፍቅር እጅግ ተሰቃየህ።" አለው። ቅዱሱ ግን "ጌታዬ ሆይ! የእኔ መከራ በአንተ መከራ ሲታሰብ ኢምንት ነውና እባክህ ስለ ስምህ ሌሎች መከራዎችን እንድቀበል ፍቀድልኝ? ገና ሕማምህን አስቤ አልረካሁምና።" አለው።

ጌታ ግን "የለም! መከራው ይበቃሃል። መጥቼ እስክወስድህ ድረስ ከአባ ብሶይ ጋር ቆይ።" ብሎት ባርኮት ዐረገ። አባ ባውላም እንደ ታዘዘው በአባ ብሶይ ገዳም ከቅዱስ ብሶይ ጋር ቆይቶ በዚህች ቀን ዐርፏል።

ይህቺውም ዕረፍቱ ለስምንተኛ ጊዜ ሆና ተቆጥራለች። የቅዱሱን ዜና የጻፈው ደቀ መዝሙሩ አባ ሕዝቅኤል ሲሆን ያሰፈረው እንባው እንደ ዥረት እየወረደ ነው።
አባቶቻችን ሊቃውንትስ ታላቁን ጻድቅ ሲያመሰግኑት እንዲህ አይደለምን!
"ውስተ ገድል ጽኑዕ ዘአልቦ ምምዐ
ወደቀ ስብአ ወተንሳእከ ስብአ።"

አምላከ አባ ባውላ በጻድቁ ላይ ያሳደረውን ፍቅሩን ያሳድርብን። ከበረከቱም ያድለን።

ጥቅምት ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ባውላ መስተጋድል
፪.አባ ሕዝቅኤል ጻድቅ
፫.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ሐናሲ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፮.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

"እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ። መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል። ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?"
(ማቴ. ፲፮፥፳፬-፳፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ ወአባ ጰንጠሌዎን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ ሊቅ <3

በዘመነ ሐዋርያት ከነበሩና አስደናቂ ታሪክ ከነበራቸው ቅዱሳን አንዱ ይህ አባት ነው። ቅዱስ ዲዮናስዮስ በትውልዱ አረሚ (ግሪካዊ) የሆነ ፈላስፋ ከነ አሪስቶትል ሲያያዝ የመጣውን ፍልስፍና ጨርሶ በማጥናቱ ርዕሰ ሊቃውንት (የፈላስፎች አለቃ) የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር።

በግሪክ አቴና (ATHENS) ለነበሩ ፈላስፎችም ሁሉ የበላይ ሲሆን በአርዮስፋጐስ (ሐዋ. ፲፯) ታላቁ ሰው እርሱ ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እድሜው ገና ወጣት ነበር። ቅዱስ ዲዮናስዮስ ፈላስፋ ስለ ሆነ ቅሉ ይመራመር ነበር።

ይልቁኑ ስለ እውነተኛው አምላክ ያስብ ነበር። በግሪክ ምድር ከሚመለኩ ሁለት መቶ ሃምሳ አማልክት መካከል ቁም ነገር አልተገኘምና። ነገር ግን አንድ ቀን ዓለም በተፈጠረች በአምስት ሺህ አምስት መቶ ሠላሳ አራት ዓመት መጋቢት ፳፯ ቀን በዕለተ ዓርብ ስድስት ሰዓት ላይ ምድር ተናወጠች፣ ፀሐይ ጨለመች፣ ጨረቃ ደም ሆነች፣ ከዋክብትም ረገፉ።

በዚህ የተደናገጡ የአቴና (ATHENS) ነዋሪዎችና ፈላስፎች ወደ ዲዮናስዮስ ተሰብስበው "መምህራችን የተፈጠረውን ነገር መርምረህ አስረዳን?" አሉት።
ዲዮናስዮስም ባለው ጥበብ ባሕሩን፣ የብሱን፣ ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ ከዋክብትን መረመራቸው። "ወረከቦሙ ኅዱዓነ" እንዲል በቀደመ ቦታቸው አገኛቸው። ግራ ቢገባው እንቅልፍ ከዓይኑ ተከለከለ።

ከዚያም ወደ ቤተ መዛግብቱ ገብቶ መጻሕፍትን ሲያገላብጥ "አርስጣላባ" የሚባል ግዙፍ መጽሐፍ አግኝቶ ቢገልጠው "እልመክኑን" የሚል ጽሑፍ አገኘ። ወደ ውጪ ወጥቶ በሕዝቡና ጠቢባኑ ፊት ልብሱን ቀድዶ አለቀሰ።
እነርሱም ደንግጠው "ምነው መምህራችን? ምን ሆንህ?" ቢሉት "የማይታየው አምላክ ቢወርድ በምቀኝነት ገደሉት የሚል ጽሑፍ አገኘሁ።" አላቸው።
"እልመክኑን" ማለት "የማይታይ አምላክ" ማለት ነውና።
"ዘኢያስተርኢ ኅቡዕ እስመ አስተርአየ ለነ
እሳት በላኢ አምላክነ" እንዲል።

ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን (ተማሪዎቹን) ጠርቶ (ኡሲፎስና ኡርያኖስ ይባላሉ።) "እልመክኑን" የሚለውን ስም "ከቤተ ጣዖቱ በር ላይ ለጥፉት።" ብሏቸው ለጠፉት። በእንዲህ ያለ መንገድ አሥራ አራት ዓመታት አልፈው ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን እየሰበከ አቴና ደረሰ። ዘመኑም በ፵፰ ዓ.ም ነበር።

ወደ ከተማዋ ሲገባ በጣዖት ቤቱ በር ላይ የተለጠፈውን ጽሑፍ ተመለከተና ያስተምራቸው ያዘ። ትምህርቱን የሰሙ ጠቢባኑና ሕዝቡ ሐዋርያውን ይዘው ወደ ዲዮናስዮስ ፊት አቀረቡት። "ምንድን ነው በደሉ?" ቢላቸው "አዲስ አምላክን ሲያስተምር አግኝተነዋል።" አሉት።

ቅዱስ ጳውሎስም "እኔ አዲስ አምላክን የምሰብክላችሁ አይደለሁም። ይልቁኑ ከቀድሞም የፈጠራችሁ ቀጥሎም የሞተላችሁ እናንተም 'እልመክኑን' ብላችሁ ሳታውቁት ታመልኩት የነበረውን ጌታ እንጂ። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።" አላቸው።

ዲዮናስዮስም ቅዱስ ጳውሎስን "ለዚህ ምን ምልክት አለህ?" ቢለው "የዛሬ አሥራ አራት ዓመት መጋቢት ፳፯ ቀን በዕለተ ዓርብ ስድስት ሰዓት ላይ ታላላቅ ተአምራት የተደረጉ አይደለምን! እነዚህ ሁሉ የተደረጉት በስቅለቱ ጊዜ ነው።" ሲል መለሰለት።

ዲዮናስዮስም ፈጥኖ በክርስቶስ አመነ። የአካባቢው ጠቢባንና ሕዝቡም አምነው ከመሪያቸው ጋር ተጠመቁ። ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱስ ዲዮናስዮስን አስተምሮ የአቴና የመጀመሪያው ጳጳስ አደረገው። ቅዱሱም ክርስቲያኖችን ያበዛ መንጋውንም ያጸና ዘንድ ብዙ ተጋ።

በተለይ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩ ታዋቂ ደራስያን አንዱ ሆነ። በርካታ ድርሰቶችንም በመንፈስ ቅዱስ ደረሰ። ዛሬ ድረስ እንኳ ሃይማኖተ አበው ውስጥ የሚገኘው ድርሰቱ (ዘዲዮናስዮስ) ጣዕሙ ልዩ ነው። ቅዱሱ ለብዙ ዘመናት ለወንጌል አገልግሎት ተግቶ በዚህች ቀን የአካባቢው አገረ ገዥ አንገቱን አስቆርጦት ሰማዕት ሆኗል።

የሚገርመው ግን ሲገድሉት በቦታው ሰው ስላልነበረ ቅዱሱ ተነስቶ ተቆርጣ የወደቀች ራሱን አነሳት። በጐኑ አቅፎም ደቀ መዛሙርቱ እስካሉበት ሒዶ በፊታቸው ዘንበል አለ። ምዕመናንም እያለቀሱና እየዘመሩ ከአርድእቱ ኡሲፎስና ኡርያኖስ ጋር ቀብረውታል። እነርሱም አብረውት ተሰይፈዋልና።

<3 አባ ጰንጠሌዎን ዘጾማዕት <3

ታላቁ ጻድቅ፣ ሰባኬ ወንጌልና ገዳማዊ አባ ጰንጠሌዎን የተስዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳን መሪ (አባት) ናቸው። ጻድቁ ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ቢሆንም ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮጵያ ነው።

ወላጆቻቸው በሮም ቤተ መንግስት የቀኝ መንበር ያላቸው ክቡራን ቢሆኑም ልጃቸውን "ይማር" ብለው ወደ ገዳም ከተቷቸው። በገዳም ትምህርቱን ከጠነቀቁ በኋላ በዚያው ጠፍተው ወደ ግብጽ ወረዱ፤ በዚያም መነኮሱ።

እድሜአቸው እየገፋ ሲሔድ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስምንቱን ቅዱሳን ሰብስበው በአቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) መሪነት ወደ ሃገራችን መጡ። በአራት መቶ ሰባዎቹ አካባቢ የነበረው ንጉሥ አልዓሜዳም በክብር ተቀብሎ አክሱም ውስጥ "ቤተ ቀጢን" የሚባል ቦታን ሰጣቸው።

ዘጠኙ ቅዱሳን በአንድነት ቀን ቀን ወንጌልን ሲያስተምሩ ውለው ሌሊት ሲጸልዩና መጻሕፍትን ሲተረጉሙ ያድሩ ነበር። ነገር ግን ለየብቻቸው መኖራቸውን መንፈስ ቅዱስ ስለ ወደደ ሁሉም በየራሳቸው ገዳማትን መሠረቱ።

አባ ጰንጠሌዎንም ከአክሱም ከተማ በላይ ከደብረ ቆናጽል ጐን ወደሚገኝና 'ጾማዕት' ወደ ሚባል ረዥም ተራራ ወጡ። ቦታው ዛሬ "እንዳባ ጰንጠሌዎን" ይባላል። በዚያም አስቀድመው ለወንጌል አገልግሎት እየተጉ ድውያንን ፈወሱ፣ ሙታንን አስነሱ፣ አጋንንትን አሳደዱ። ብዙ ተአምራትንም አደረጉ። እንዲያውም አንድ ቀን ወይራውን በጧት ተክለው በሠርክ ትልቅ ዛፍ ሆነላቸው። ከዚያ ዘንጥፈው እሳቱን በቀሚሳቸው ላይ አፍመው ማዕጠንት አሳርገዋል።

የሚገርመው ያ ዛፍ ዛሬም ድረስ ለምስክርነት ቁሟል። እኛም ሳይገባን ሔደን በዓይናችን አይተነዋል። አምላከ ቅዱሳን ግሩም ነው! በመጨረሻ ዘመናቸው ግን ጻድቁ አምስት ክንድ ርዝመት ባላት ጾማዕት (በዓት) ውስጥ ገብተው ቆሙ። ለአርባ አምስት ዓመታት ሳይቀመጡና ሳይተኙ በእንባ ቢጸልዩ ቅንድባቸው ተላጠ። አካላቸውም በአጥንቱ ብቻ ቀረ።

በስድስተኛው ክፍለ ዘመንም በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም መጥቶ "ወዳጄ! ስምህን የጠራ መታሰቢያህን በእምነት ያደረገውንም ሁሉ እምርልሃለሁ።" አላቸው። ያን ጊዜ አጥንቶቻቸው ተወዛወዙና ነፍሳቸው በክብር ዐረገች። ከዚህ አስቀድሞም ንጉሡን አፄ ካሌብን አባት ሆነው ያመነኮሱት እርሳቸው ናቸው።

አምላከ አበው የወጡ ወገኖቻችንን ሁሉ በሰላም ይመልስልን። ከክብረ ቅዱሳንም አይለየን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሃ እና ለቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሃ <3

እነዚህ ነገሥታት ሞገሶቻችን ብርሃኖቻችን ናቸውና ደስ እያለን እንወዳቸዋለን፤ እናከብራቸዋለን። ሥላሴ ቢመርጧቸው ዛሬ ላለንበት ሕይወት መሠረቱን ጥለው አልፈዋልና።

ሁለቱ ቅዱሳን ነገሥታት መንትያዎች ሲሆኑ ወላጆቻቸው ንጉሥ ታዜር /አይዛና/ ሠይፈ አርዕድ እና ንግሥት አሕየዋ /ሶፍያ/ ይባላሉ። ንጉሡና ባለቤቱ ልጅ ቢያጡ ወደ እግዚአብሔር ለመኑ። ፈጣሪም በቅዱስ ሚካኤል አብሳሪነት ሁለት ዕንቁዎችን አስረከባቸው።

ንግሥት አሕየዋ (ሶፍያም) መጋቢት ፳፱ ቀን በ፫፻፲፩ ዓ/ም ጸንሳ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን በ፫፻፲፪ ዓ/ም ሁለቱን ቅዱሳን ወልዳቸዋለች። "አምላክ ሽሙጥን አራቀልኝ።" ስትልም "አዝጓጉ" ብላቸዋለች። እነዚህ ሁለት ፍሬዎች በልጅነታቸው ከወቅቱ ሊቀ ካህናት እንበረም ኦሪቱን ጠንቅቀው ተምረዋል።

ከእግዚአብሔር የተሰጡ ናቸውና በ፲፪ ዓመታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተዋል። ትንሽ ቆይቶ ግን አባታቸው ታዜር በማረፉ ሕዝቡ ሁለቱን ቅዱሳን "ንገሡልን?" አሏቸው። እነርሱም "እኛ የፈጣሪ አገልጋዮች ነንና አንችልም።" በማለታቸው ለተወሰነ ጊዜ እናታቸው አስተዳደረች።

ቆይቶ ግን ቅዱስ ሚካኤል ለሊቀ ካህናቱ እንበረም "የፈጣሪ ፈቃዱ ስለ ሆነ አትዘኑ። ሁለታችሁም በአንድ ዙፋን ላይ ንገሡ፤ ታላቅ ጸጋ ለሃገሪቱ ይሆናል በላቸው።" አለው።
ሊቀ ካህናቱም የታዘዘውን ተናግሮ በአሥራ ዘጠኝ ዓመታቸው ሁለቱንም በአንድ ዙፋን ላይ "ነገሥተ ኢትዮጵያ" ሲል አስቀምጦ ቀባቸው። ስማቸውን "ኢዛና" እና "ሳይዛና" አላቸው። ቅዱሳኑ እንደ ነገሡ ቀዳሚ ሥራቸው የቀናችውን ሃይማኖት መፈለግ ሆነ።

በወቅቱ ፍሬምናጦስ (የኋላው አቡነ ሰላማ) በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የቅርብ አማካሪ ነበርና ጠርተው ተጨዋወቱት። "አንተ ወንድማችን! ክርስቶስ ይወርዳል፣ ይወለዳል ተብሎ የተቆጠረው ሱባኤ እኮ አልፏል። ምነው ቀረሳ? በእርግጥ ምሥጢሩን ንገረን?" አሉት።

እርሱም አትቶ፣ አመሥጥሮ ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት አምላክ ሰው መሆኑንና ዓለምን ማዳኑን አስተማራቸው። "አጥምቀን?" ቢሉት "አልችልም" አላቸው። እነርሱም ከብዙ ስጦታ ጋር ወደ ግብጽ ላኩት።

ቅዱስ አትናቴዎስም ፍሬምናጦስን "አቡነ ሰላማ" ብሎ ከብዙ መጻሕፍት ጋር ላከው። በመጀመሪያ ኢዛናና ሳይዛና ተጠመቁ። ስማቸውም "አብርሃ ወአጽብሃ" ተባለ። ቀጥሎም ሠራዊቱና ሕዝቡ ተጠመቀ።

ሃገራችንም በእነዚህ ቅዱሳን አማካኝነት ከጨለማ ወደ ብርሃን መጣች። የክርስትና ደሴት ሆነች። ሃገረ እግዚአብሔርነቷንም አጸናች። ቅዱሳኑ ከዚህ በኋላ በሞገስ ክርስትናን ያስፋፉ ዘንድ ደከሙ። ከመቶ ሃምሳ አራት በላይ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንጹ አብዛኞቹ ፍልፍል ነበሩ።

በተለይ ግን በአክሱም ከተማ ላይ ያነጿትና አሥራ ሁለት ቤተ መቅደሶች የነበሯት የጽዮን ቤተ ክርስቲያን ልናያት ትናፍቀናለች። ጌጧ፣ ብርሃኗ ውል ውል ይልብናል። ይህቺው ቤተ ክርስቲያን በአሥረኛው ክፍለ ዘመን ዮዲት ጉዲት በእሳት አውድማታለችና። መሠረቱ ግን ዛሬም አለ።

ቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሃ ግን ክርስትናን ለማስፋፋትና መንግሥትን ለማጽናት ሲሉ ከአክሱም በተጨማሪ በሽዋም ዙፋንን ዘረጉ። ለብዙ ዓመታትም አምላክ በፈቀደው መንገድ እስከ የመን ድረስ ገዙ፤ ክርስትናንም አስፋፉ።

ቅዱስ አብርሃ በተወለደ በሃምሳ ሁለት ዓመቱ በ፫፻፷፬ ዓ/ም ጥቅምት ፬ ቀን ሲያርፍ ወንድሙ ለአሥራ አምስት ዓመታት ብቻውን አስተዳድሯል። በ፫፻፸፱ ዓ/ም ደግሞ በዚሁ በጥቅምት ፬ ቀን ቅዱስ አጽብሃም በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በክብር ዐርፏል።

ከሁለቱም መቃብር ላይ ለሠላሳ ቀናት የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ ታይቷል። ጌታችንም በማይታበል ቃሉ "ስማችሁን የጠራውን፣ መታሰቢያችሁን ያደረገውንም እምርላችኋለሁ።" ሲል ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።

<3 ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ <3

ሐናንያ ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ከተቀመጠልን ከጥቂቶቹ ዋነኛው ነው። ከነገደ እሥራኤል ተወልዶ፣ በሕገ ኦሪት አድጐ፣ ከወጣትነት ዕድሜው ትንሽ እልፍ ሲል ጌታችን ወንጌልን ማስተማር ጀምሯልና ጠራው። እርሱም በበጐ ፈቃድ ተከትሎታልና ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደመረው::

ለሦስት ዓመታት ከጌታ እግር ተምሮ ከዕለተ ስቅለት በፊት ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት ነበር። ምክንያቱም ቅዱስ ሉቃስ እንደ ጻፈልን ሰብዐው አርድእት "ጌታ ሆይ! አጋንንት በስምህ ተገዙልን።" ማለታቸውን አስቀምጦልናል።
(ሉቃ. ፲፥፲፯)
ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በሃምሳኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል።

በሚያስተምር ጊዜ የሶርያዋን ደማስቆን ማዕከል አድርጐ ነበር። በኋላም አበው ሐዋርያት የዚህች ከተማ የመጀመሪያው ጳጳስ አድርገው ሹመውታል። ጌታ ባረገ በስምንተኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ የነበረው ሳውል (የኋላው ቅዱስ ጳውሎስ) ወደ ደማስቆ የተጓዘው ክርስቲያኖችን በተለይም ቅዱስ ሐናንያን ለማሠር ነበር።

ለእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ ይሆን ዘንድ መብረቅ ዓይኑን አጠፋው። ወዲያውም ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሔድ ነገረው። ከሦስት ቀናት በኋላ ጌታችን ለሐናንያ ተገልጦ አነጋግሮታል። ሳውል (ጳውሎስ) ወደ ሐናንያ የደረሰው በመሪ ነበር።

ሁለቱ እንደተገናኙ ቅዱስ ሐናንያ ሳውልን አስተማረው፣ ፈወሰው፣ አጠመቀው፣ በጐ መንገድንም መራው። በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ሐዋርያ የቅዱስ ጳውሎስ የንስሐ አባቱ ይሰኛል።
(ሐዋ. ፱፥፩-፲፱)

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን አስተማረ መከራንም ተቀበለ። በመጨረሻም በዚህ ቀን ክፉዎች ከብዙ ስቃይ በኋላ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል።

አምላከ አብርሃ ወአጽብሃ "ድሃ ተበደለ፣ ፍርድ ተጓደለ።" የሚል ዳኛ ሃይማኖቱ የቀና መሪንም ያምጣልን። የቅዱሳኑን ክብር በእኛ ላይ ያድርግልን።

ጥቅምት ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ነገሥት አብርሃ ወአጽብሃ
፪.ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ባኮስ ሰማዕት
፭.ቅዱሳን ባባ እና ማማ
፮.ቅዱስ ዮሐንስ ሕጽው

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
፪.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

"እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።
ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።"
(፩ጢሞ ፪፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥቅምት ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ሊቁ አባ ሕርያቆስ
፪.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፫.ቅድስት ቴክላ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)
፪.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
፭.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)

"......ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።"
(ይሁዳ ፩፥፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያና ወንጌላዊ ቅዱስ ሉቃስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ <3

ቅዱስ ሉቃስ፦
*ሐዋርያ ነው።
*ወንጌላዊ ነው።
*ሰማዕት ነው።
*ዓቃቤ ሥራይ (ዶክተር) ነው።
*የጥበብ ሰው (ሠዓሊ) ነው።
*ዘጋቢ (የሐዋርያትን ዜና ሕይወት የጻፈ) ነው።
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፦
በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን መነሻ አካባቢ በተወደደች የጌታ ዓመት ከእስራኤላውያን ወገኖቹ ቅዱስ ሉቃስ ተወልዷል። ያደገውም መቄዶንያ አካባቢ ነው። ጌታችን ተጠምቆ ማስተማር ሲጀምር ከተከተሉት የአምስት ገበያ ሕዝብ መካከል መቶ ሃያውን ለቤተሰብነት መምረጡ ይታወቃል።

ታዲያ እንዲጠቅም አውቆ ቅዱስ ሉቃስን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደምሮታል። ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከተከተለ በኋላ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት እየዋለ ካደረበትም እያደረ የቃሉን ትምህርት የእጆቹን ተአምራት በጥሞና ይከታተል ነበር።

ጌታችን ለዓለም ድኅነት ተሰቅሎ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ስለዚህ ቅዱስ የሚናገር አንድ የወንጌል ክፍል እናገኛለን። በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬ ላይ ከምናያቸው የኤማሁስ መንገደኞች አንዱ ይህ ቅዱስ እንደ ሆነ አባቶች አስተምረውናል።

በእርግጥ "ቀለዮጳ" የሚለው ስም በዘመኑ የብዙዎች መጠሪያ ቢሆንም እርሱም ጌታን ከመከተሉ በፊት በዚህ ስም ይጠራ እንደ ነበር ይታመናል። በወቅቱ ታዲያ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት (ሉቃስና ኒቆዲሞስ) ወደ ኤማሁስ ሲሔዱ ጌታ መንገድ ላይ ተገልጦ እያጫወታቸው አብሮ ተጉዟል።

እነርሱም ማንነቱን አላወቁምና ስለ ራሱ ለራሱ እየሰበኩለት ተጉዘዋል። ከሐዘናቸው ብዛት ማስተዋል ተስኗቸው ቀቢጸ ተስፋም ወሯቸው ነበርና መድኃኒታችን ክርስቶስ የነቢያትን ትንቢት ተረጐመላቸው።

በዚህ ጊዜም ከነገሩ ማማር ከምሥጢሩ መሥመር ጋር እየገረማቸው ልቦናቸው ይቃጠል (ይቀልጥባቸው) ነበር። "አኮኑ ይነድደነ ልበነ" እንዲል። ወደ ኤማሁስ ሲደርሱ ግን ደጐች ናቸውና "በቤት ካላደርክ ራት ካልበላህ?" ብለው ግድ አሉት።

በማዕድ ሰዓት ግን ቡራኬውን ሰጥቷቸው ቸር አምላክነቱን ገልጦላቸው ተሰወራቸው። እነርሱም በሐሴት ከኤማሁስ ተመልሰው እየሮጡ ኢየሩሳሌም ደርሰው ትንሣኤውን ሰበኩ።

የመንገዱ ርዝመትም አልታወቃቸውም ነበር። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሉቃስ እንደ ሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል።

<3 ቅዱሱ ዶክተር <3

በትውፊት ትምህርት እንደ ተማርነው ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከመከተሉ በፊት ሥራው ሐኪምነት (ዶክተር) ነበር:: በዚህም አበው "አቃቤ ሥራይ (ባለ መድኃኒት)" ይሉታል። በተሰጠው ሙያም ብዙዎችን አገልግሏል።

የጌታ ደቀ መዝሙር ከሆነ በኋላ ደግሞ "አቃቤ ሥራይ ዘነፍስ - የነፍስ ሐኪም" ተብሏል። እንዲያውም አባቶቻችን ሐዋርያትን ያክማቸው ነበር ይባላል። ከደግነታቸው የተነሳም እልፍ አእላፍ ድውያንን በተአምራት ሲፈውሱ እነርሱ ግን በስቃይ ይኖሩ ነበር።
ሕመማቸው ሲጠናባቸው ግን ቅዱሱ ዶክተር ሉቃስ ይራዳቸው ነበር። ይሕንንም ቅዱስ ጳውሎስ በቆላስይስ መልእክቱ ላይ "የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ፣ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።" ሲል ገልጾታል።
(ቆላ. ፬፥፲፬)

<3 ዘጋቢው ሐዋርያ <3

ቅዱስ ሉቃስ እንደ ዛሬው ነገሮች ምቹ ባልነበሩበት ዘመን እጅግ አድካሚ የሆነ ጉዞ አድርጐ የሐዋርያትን ዜና ሕይወት ዘግቦልናል። ልክ ወንጌሉን ለታኦፊላ (ቴዎፍሎስ) ደቀ መዝሙሩ እንደ ጻፈለት ግብረ ሐዋርያትንም ለእርሱ በትረካ መልክ አቅርቦለታል።

ሲጽፍለትም "ሰማሁ" እያለ ሳይሆን አብሮ እያለ ያየውንና የተሳተፈበትን ነው። አተራረኩም በአንደኛና በሦስተኛ መደብ አድርጐ እያቀያየረ ነው። ማለትም አንዳንዴ "እኛ" እያለ ሌላ ጊዜ ደግሞ "እነርሱ" እያለ ነበር የሚተርክለት።

መጽሐፉም ሃያ ስምንት ምዕራፎች ሲኖሩት በጌታ ዕርገት ጀምሮ በኢየሩሳሌምና በአሕዛብ የነበረውን ስብከተ ወንጌል ገልጦ የቅዱስ ጳውሎስን ጉዞዎች በሰፊው ዳስሶ ይጠናቀቃል።

<3 ወንጌላዊው ሐዋርያ <3

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌልን እንዲጽፉ ከተመረጡ (ከተፈቀደላቸው) ሐዋርያት አንዱ ነው። በቤተ ክርስቲያንም "ዘላሕም" እየተባለ ይጠራል። ለዚህም ምክንያቱ፦
፩.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት በላምና በአህያ መካከል መወለዱን በመጻፉ።
፪.ጌታችንን "መግዝአ ላሕም - የሚታረድ ሜልገች (ላም)" ብሎ በመግለጹ እና
፫.ከአራቱ እንስሳ (ኪሩቤል) አንዱ (ገጸ ላሕም) ይራዳው ይጠብቀውም ስለ ነበር ነው።

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው ጌታ ባረገ በሃያ ሁለተኛው ዓመት ሲሆን ይኼውም በ፶፮ ዓ/ም አካባቢ ማለት ነው። ሲጽፍም ብቻውን አልነበረም። ልክ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ጋር እንደ ሆነው ሁሉ ቅዱስ ሉቃስም የጻፈው ከብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ጋር ነው። ምክንያቱም ለረዥም ዓመታት አብረው ለስብከተ ወንጌል ተጉዘዋልና።

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን ሲጽፍ በነ ዘካርያስ ቤተሰብ ጀምሮ ብሥራተ ገብርኤልን፣ ክብረ ድንግል ማርያምን፣ የጌታን ልደት፣ እድገት፣ መጠመቅ፣ ማስተማር፣ መሰቀል፣ መሞት፣ መነሳትና ማረግ በቅደም ተከተል ይተርክልናል።

<3 ጥበበኛው (ሠዓሊው) ሐዋርያ <3

ቅዱስ ሉቃስን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች ሌላኛው ደግሞ ጐበዝ ሠዓሊ የነበረ መሆኑ ነው። በሐዲስ ኪዳንም የመጀመሪያውን የእመቤታችንን ሥዕል (ምስለ ፍቁር ወልዳን) የሣለው እሱ ነው።

አንድ ቀን የአምላክ እናት ባለችበት ከጌታ አስፈቅዶ የሣላት ሥዕለ አድኅኖ ሥጋን የለበሰች፣ ከፊቷ ወዝ የሚወጣ፣ የምታለቅስ፣ ስትወጋ የምትደማና ድውያንን የምትፈውስ ሆና ተገኝታለች። ይህች ሥዕል ዛሬ ሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አለች ይባላል።

<3 ሰማዕቱ ሐዋርያ <3

ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ባለ ሕይወት ሲመላለስ በትጋት (ያለ ዕረፍት) ወንጌልን እየሰበከ ነበር። በ፷፮ እና በ፷፯ ዓ/ም ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ በኔሮን ቄሣር እጅ ሲገደሉ የሮም ግዛት ክርስቲያኖች ኃላፊነት በእርሱ ላይ ነበረ።

ከወንጌሉና ግብረ ሐዋርያቱ ባለፈ በመልእክታት አንድም እየዞረ ክርስቲያኖችን አጸና፤ አሕዛብንም አሳመነ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ዝናውን የሰማው ኔሮን ሊገድለው ፈለገ። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሉቃስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሲላስ የሚባለውን ሽማግሌ መርጦ መጽሐፎቹን ሁሉ አስረከበው።

በድፍረትም ወደ ኔሮን ቄሣር ቀርቦ ተናገረው። ንጉሡም "ክርስቶስን አምልኩ የምትል ቀኝ እጅህ መቆረጥ አለባት።" ብሎ እጁን ከትክሻው በሰይፍ ለይቶ መሬት ላይ ጣለው። ሁሉ ሰው ሲደነግጥ ቅዱሱ ተጐንብሶ የወደቀች እጁን አነሳትና እንደ ነበረችው አደረጋት።

በዚያ የነበሩ አሕዛብም "ግሩም" አሉ። መልሶ ግን "አሁን እጄ ሥራዋን ስለ ጨረሰች አልፈልጋትም።" ብሎ እንደ ገና ለይቶ ጣላት።
"ከመ ያርኢ ኃይለ ቅድመ ኔሮን ወተዓይኑ
አስተላጸቃ ወሌለያ ለምትርት የማኑ
እስመ ላዕሌሁ ተሰውጠ ለክርስቶስ ሥልጣኑ።" እንዲል።

በዚህ ጊዜም ይህንን ድንቅ ያዩ አራት መቶ ሰባ ሰባት ያህል አሕዛብ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተሰይፈዋል። የስብከት ዘመኑም ከሠላሳ ስድስት ዓመታት በላይ ነው።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር እና ለቅዱስ ኤልሳዕ ነቢይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር <3

በቤተ ክርስቲያን ያሉ አበው ሊቃውንት እንደሚሉት ከቅዱሳን በቁመቱ የአባ አርሳኒን ያክል ረዥም አልነበረም። እርሱ እንደ ዝግባ ቀጥ ያለ ነበር። በዚያው ልክ ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስን (ዛሬ የምናከብረውን) ያህል አጭር አልነበረም። በዚህ ምክንያት ይሔው ለዘላለም "ዮሐንስ ሐጺር - አጭሩ አባ ዮሐንስ" ሲባል ይኖራል።

ሊቃውንትም ቁመቱንና ቅድስናውን በንጽጽር ሲገልጡ፦
"ሰላም ሰላም ዕብሎ በሕቁ
ለዮሐንስ ሐጺር ዘነዊኅ ሒሩተ ጽድቁ" ይላሉ። "ቁመቱ እጅግ ያጠረ ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ ቅዱስ ዮሐንስን ሰላም ሰላም እንለዋለን።" እንደ ማለት ነው።

ቅዱሱ የተወለደው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ነው። ወላጆቹ ምንም ከሥጋዊ ሃብት ድሆች ቢሆኑም ባለ መልካም ክርስትና ነበሩና በጐውን ሕይወት አስተምረውታል። ወደ ምናኔ የገባው ገና በአሥራ ስምንት ዓመቱ ሲሆን የታላቁ አባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር ሆኖ ተጋድሎንና ትሕርምትን ተምሯል።

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩ ቅዱሳን ከቁመቱ ባሻገር በትሕትናው፣ በትእግስቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር። አባ ባይሞይ ይጠራውና ያለ ምንም ምክንያት ደብድቦ ያባርረው ነበር። እርሱ ግን "ምን አጠፋሁ?" ብሎ እንኳ ሳይጠይቅ "አባቴ ሆይ! ማረኝ?" እያለ ከእግሩ ሥር ይወድቅ ነበር።

ለብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ሲደበድበው እርሱም እርሱው ተደብድቦ እርሱው ይቅርታን ሲጠይቅ ኖረ። አንድ ቀን ግን እንደ ልማዱ ሊገርፈው ሲሔድ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ከበውት አይቶ ደንግጦ ተመልሷል።

አባ ባይሞይ ይሕንን ሁሉ የሚያደርገው ጠልቶት ወይ ክፉ ሆኖ አይደለም። አንድ ሰው የሌላኛውን ግፍ መቀበል ካልቻለ ሰይጣንን ድል አይነሳም የሚል ትምህርት ስለ ነበረ ነው እንጂ።

አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መምህሩ ቀርቦ "አባቴ ጅብ ካገኘሁ ምን ላድርግ?" ሲል ጠየቀው። (የአካባቢው ጅብ መናጢ ነበር።) አባ ባይሞይ ግን "ይዘህ አምጣልኝ።" አለው። ትዕዛዝ ነውና ቅዱሱ ወደ በርሃ ወርዶ ጅብ አልምዶ ይዞለት መጥቷል።

ሌላ ቀን ደግሞ አባ ባይሞይ ቅዱስ ዮሐንስን ጠራውና ተፈልጦ የወደቀ ደረቅ እንጨት ሠጠው። "ምን ላድርገው አባ?" አለው። "ትከለውና እንዲያፈራ አድርገው። ከዚያ አምጥተህ አብላኝ።" ሲል መለሰለት። ይህ ነገር ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ መሆኑን እያወቀ ቅዱስ ዮሐንስ "እሺ" ብሎ ወስዶ ተከለው።

ከዚያም ለሁለት ዓመታት ሳይታክት ውኃ አጠጣው። ውኃውን የሚያመጣበት ቦታ ደግሞ አሥር ኪሎ ሜትር ያህል ከገዳሙ ይርቅ ነበር። ቅዱሱ ላቡን እያፈሰሰ አሁንም ማጠጣቱን ቀጠለ።

በሦስተኛው ዓመት ግን ለምልሞ አበበ ደግሞም አፈራ። ካፈራው በኩረ ሎሚም ወስዶ ለመምህሩ "አባቴ! እንካ ብላ።" ብሎ ሰጠው። አባ ባይሞይ ግን ማመን አልቻለም። እጅግ አደነቀ፤ አለቀሰም።

ወዲያው ያን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት "ንሱ ብሉ፤ በረከትንም አግኙ። ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው።" አላቸው።
ቅዱስ ዮሐንስ አባ ባይሞይ ቢታመም ለአሥራ ሁለት ዓመታት አስታሞታል።

መምህሩ ከማረፉ በፊትም መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስን እጅ አስጨበጣቸው። "ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመልአክ እጅ ነው።" ብሏቸው ዐርፏል። ቅዱስ ዮሐንስም ከዓመታት ቆይታ በኋላ የገዳሙ አበ ምኔት ሆኖ አገልግሏል። ብዙ ነፍሳትንም ለቅድስና ማርኳል።

መላእክት ንጽሕናው ደስ ስለሚያሰኛቸው አብረውት ይውሉ ነበር። ሲተኛም በተራ በተራ ክንፋቸውን ያለብሱት ነበር። ምጽዋትን በጣም ስለሚወድ ሰፌድ እየሰፋ ይሸጥና ገንዘቡን ለነዳያን ያካፍል ነበር።

አንድ ቀን እንደ ልማዱ ወደ ገበያ ወጥቶ ሳለ ተደሞ (ተመስጦ) መጣበት። ሰማያት ተከፍተው ቅዱሳን ሊቃነ መላእክት ሚካኤልና ገብርኤል በግርማ በጌታ ፊት ቆመው ተመለከተ።

"እጹብ፣ እጹብ" እያለ ሲያደንቅ አንድ ገዢ መጥቶ "ባለ እንቅብ ዋጋው ስንት ነው?" ቢለው "እኁየ ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ ገብርኤል - ከሚካኤልና ከገብርኤል ማን ይበልጣል?" ብሎታል። ገዢውም ደንግጦ "እብድ መነኩሴ" ብሎት ሔዷል።

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ወደ ባቢሎን (የአሁኗ ኢራቅ) ሒዶ ከተመለሰ በኋላ በበርበሮች ምክንያት ከአስቄጥስ ወደ ቁልዝም ተሰዷል። በዚያም በአባ እንጦንስ በዓት ውስጥ ዐርፏል። ለአራት መቶ ዓመታት በዚያው ቆይቷል።

በ፰፻፳፭ ዓ/ም ግን በአባ ዮሐንስ ፓትርያርክ ዘመን ክቡር ሥጋው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ተመልሷል። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ሥጋ በተገናኙ ጊዜ ግሩም ተአምር ተደርጓል። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲገባም ታላቅ የብርሃን ጐርፍ ሲፈስ ታይቷል።

ሰማያዊ መዓዛም አካባቢውን ሞልቶታል። ከጳጳሳቱ አንዱ እባረካለሁ ብሎ የቅዱስ ዮሐንስን ሥጋ ቢገልጠው አካባቢው ተናወጠ። መባርቅትም (መብረቆች) ተብለጨለጩ። ደንግጠው ቶሎ ቢያለብሱት ጸጥታ ሆኗል። በዚህ ሁሉ ደስ ያላቸው አበው ቅዱሱን በዝማሬ ሲያወድሱት ውለዋል። ቅዱሱ ያረፈው ዛሬ ነው።

<3 ቅዱስ ኤልሳዕ ነቢይ <3

ከነቢያተ እሥራኤል አንዱ፣
ከእርሻ ሥራ ቅዱስ ኤልያስን የተከተለ፣
መናኔ ጥሪት የተባለ፣
በድንግልና ሕይወት የኖረ፣
የታላቁ ነቢይ ኤልያስ መንፈስ እጥፍ የሆነለ፣
እጅግ ብዙ ተአምራትን ያደረገ፣
አንዴ በሕይወቱ አንዴ በአጽሙ ሙታንን ያስነሳ ታላቅ ነቢይና አባት ነው።

ቅዱስ ኤልሳዕ በጣም ረዥም፣ ራሱ ገባ ያለ (ራሰ በራ)፣ ቀጠን ያለ፣ ፊቱ ቅጭም ያለ (የማይስቅ) ሽማግሌ ነበር።

አምላከ ቅዱሳን የሐጺር ቅዱስ ዮሐንስን መታዘዙን፣ ትሕትናውን፣ ትእግስቱንና ቅንነቱን ያድለን። በበረከቱም ይባርከን።

ጥቅምት ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር
፪.ቅዱስ ኤልሳዕ ነቢይ
፫.አባ ባይሞይ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፪.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፫.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፬.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
፭.ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት

"እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ 'የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል።' በሉ።"
(ሉቃ ፲፯፥፲)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ እና ለቅዱስ ዮሐንስ ዘጸይለም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ንጉሥ <3

የሰው ልጅ "ንጉሥ" ተብሎ "ቅዱስ" መባል ግን ምን ይደንቅ! ይህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ መሪ ንጉሥ ሲሆን እንደ ደናግል ድንግል፣ እንደ ባሕታውያን ገዳማዊ፣ እንደ ቀሳውስት ካህን፣ እንደ ሐዋርያት ሰባኪ ሆኖ መገኘቱ ይደንቃል።

የሚያሳዝነው ይህንን እንቁ ንጉሣችን ብዙ ኢትዮጵያውያን መዘንጋታችን ብቻ ነው። የላስታ አካባቢ እጅግ የታደለችና የተቀደሰች ናት። እንደ ሌሎቹ የሃገራችን ክፍሎች ሁሉ እሷም መካነ ቅዱሳን ናትና።

ቅዱስ ይምርሐ የዘር ሐረጉ ከዛግዌ ነገሥታት ሥር ሲሆን አባቱ ግርማ ስዩም ይባላል። ይኸውም በመጀመሪያው ሺህ ዓመት (Millenium) መጠናቀቂያ ላይ ነግሶ የነበረ ነው። ዣን ስዩም (የላሊበላ አባት)፣ ጠጠውድም (ንጉሡ) እና ግርማ ስዩም ወንድማማቾች ናቸው።

ቅዱሱ ሲወለድ አባቱ በሕይወት አልነበረም። እናቱና የወቅቱ አባቶች "ይምርሐነ ክርስቶስ - ክርስቶስ ይምራን።" አሉት። ገና ከሕፃንነቱ መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና ረቡዕና ዓርብ ቀን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የእናቱን ጡት አይቀምስም ነበር። እናቱ ግን ባለመረዳት ትጨነቅ ነበር።

የወቅቱ ንጉሥ ጠጠውድም "ከእኔ ቀጥሎ የሚነግሠውን ባወኩት።" እያለ ሲመኝ በሕልሙ "ሕፃኑ ይምርሐ ነው።" የሚል በማየቱ ሕፃኑን አስመጣው። ከደም ግባቱ የተነሳም ቅንዓት አድሮበት አማካሪዎቹን "ምን ላድርገው?" አላቸው።

እነርሱም "ብትገድለው እግዚአብሔር በደሙ ይጠይቅሃል። ግን እንዳይወርስብህ ከፈለክ እረኛ አድርገው።" አሉት። (የዋሃን! ቅዱስ ዳዊት ከእረኝነት መጠራቱን ዘንግተውታል።) ከሰባት ቀናት በኋላ ግን መጥተው "ንጉሥ ሆይ! ፈጣሪ ካለ የሚቀር ነገር የለምና በቃ ዝም ብለህ ግደለው።" አሉት።

በዚያች ሰዓት ቅዱስ ሩፋኤል ከሰማይ ወርዶ እናቱን "ይምርሐን ስጭኝ።" አላት። እናት ናትና ጨነቃት። መልአኩ ግን እንደሚጠብቀው ቃል ገብቶላት ከላስታ ነጥቆ ኢየሩሳሌም አደረሰው።

ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስም ለዓመታት ተምሮ ዲቁናን ተቀበለ። በኢየሩሳሌም አካባቢም በጾምና በጸሎት ተወስኖ ፈጣሪውን እያገለገለና ወንጌልን እየሰበከ የወጣትነት እድሜውን ገፋ።

አንድ ቀን ግን መድኃኒታችን ተገልጦ "ወዳጄ ይምርሐ! ሚስት አግብተህ ቅስና ተቀብለህ አገልግለኝ።" አለው። ቅዱሱ ይህንን ሲሰማ አዝኖ "ጌታዬ! የእኔስ ፈቃዴ በድንግልና አገለግልህ ዘንድ ነው።" አለው። ጌታችንም "ግዴለህም! ሁሉም አይቀርብህም።" ብሎ አንዲት ሕዝባ የምትባል ደግ እስራኤላዊት ጠቆመው።

ቅዱስ ይምርሐም ቅድስት ሕዝባን በተክሊል አግብቶ ቅስናን ተቀበለ። ግሩም የሚያሰኘው ግን ሁለቱ ቅዱሳን ከአርባ ዓመታት በላይ በትዳርም በድንግልናም መኖራቸው ነው። "ለሚያምን ሁሉ ይቻላል።" ይል የለ ቅዱስ መጽሐፍ።

ቅዱሳኑ ወዲያው ለአገልግሎት ወደ ግብጽ ወረዱ። በዚያ ለጥቂት ዓመታት እንደቆዩ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ፈለገ። አንድ ቀን ሕዝቡ ተሰብስበው ጸሎተ ኪዳንን ሲመራ "እግዚአብሔር አብ ወሐቤ ብርሃን - ብርሃንን የምትሰጥ እግዚአብሔር አብ" ከሚል ሲደርስ ወደ ሰማይ ጮኸ።

ከሰማይም "አቤት ልጄ ሆይ!" የሚል መልስ መጣለት። ይምርሐም "ምነው ጌታዬ በሰው ሃገር ረሳኸኝ?" ቢለው "አልረሳውህም። ይልቁኑ ሊገድልህ የሚፈልግህ ንጉሥ ሙቷልና ሒደህ ንገሥ።" ሲል አዘዘው።

ቅዱሱም ሚስቱን ሕዝባን ይዞ ላስታ ሲደርስ ሕዝቡ በዕልልታ ተቀብሎ ወዲያው አነገሠው። በዚያም ለአሥራ አምስት ዓመታት ቅዱስ ሩፋኤል እየተራዳው ሕብስትና ጽዋዕ ከሰማይ እየወረደለት ቀድሷል፤ ሃገሪቱንም መርቷል።

አንድ ቀን ግን ክፉ መካሪዎች "ተጨማሪ ሚስት አግባ።" ቢሉት ተቆጣቸው። በኋላ ደግሞ "ለምን ተቆጣሁ።" ብሎ አዘነ። ስለዚህም ሃሳቡ ሰማያዊው ስጦታ ቀረበት።

እያለቀሰ ጌታን ቢማጸን ጌታችን "ስላሰብከው ክፉ ሃሳብ (ለምን ተቆጣሁ ማለቱ ወደ ምክራቸው ማዘንበሉን ያሳይ ነበርና።) ይቅር ብየሃለሁ። ነገር ግን እኔ ወደ ማሳይህ ቦታ ካልሔድክ ሁለተኛ አይወርድልህም።" አለው።

ቅዱሱ ለጊዜው ትንሽ ቢከራከርም "እሺ" ብሎ በቅዱስ ሩፋኤል መሪነት ዛሬ ወደ ምናውቀው አካባቢው ሔደ። በዚያም አራዊትን በጸሎቱ አድክሞ፣ መሠሪዎችን አስተምሮ፣ ሕዝቡንም አሳምኖ አጠመቃቸው።

ጌታም "ከኢየሩሳሌም በደመና እየጫንክ በዚህ ባሕር ላይ ቤቴን ሥራልኝ።" አለው። ቅዱስ ይምርሐም መስከረም ፲፫ ቀን (በበዓለ ባስልዮስ) ጀምሮ ሰኔ ፳ (በበዓለ ሕንጸታ) ፈጸመና ታቦተ ገብርኤልን ሰኔ ፳፩ ቀን ቀደሰው።

ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ በዚያ ቦታ እየቀደሰ ለሃያ አምስት ዓመታት ሃገሪቱን አስተዳደረ። አንድ ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ለንጉሡ ከሰማይ ሕብስትና ጽዋዕ ሲያወርድለት አንድ ባሕታዊ አይቶ "ለምን?" ብሎ ተቆጣ። መልአኩ ግን የንጉሡን ክብር ነግሮ "እየዞርክ ስበክ።" ብሎታል።

በዚያ ባሕታዊ ስብከትም ከመላው ዓለም ብዙ ሺህ ሰዎች መጥተው ቅዱስ ይምርሐን "ቀድሰህ አቁርበን?" ብለው ለምነውታል። ቅዱሱም ሲያቆርባቸው በመምሸቱ ፀሐይን አቁሟታል።

ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ እንዲህ ባለ ጣዕመ ሕይወት ኑሮ ለአርባ ዓመታት ሃገራችንን አስተዳድሮ ጥቅምት ፲፱ ቀን ዐርፎ በዚያው ሥፍራ ተቀብሯል። ጌታችንም "መታሰቢያህን ያደረገውን ደጅህን የረገጠውን እምርልሃለሁ።" ብሎታል።

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ዘጸይለም <3

በምድረ ግብጽ በዘመነ ጻድቃን የተነሳው ታላቁ አባ ዮሐንስ "ሐዋርያዊ ጻድቅ" ይባላል። ወላጆቹ ደጋግ፣ የተወለደው በጾምና ጸሎት፣ ያደገውም በሥርዓት ነው። በወጣትነቱ ከቤተሰቦቹ ጠፍቶ በርሃ ገብቶ የአባ ስምዖን ደቀ መዝሙር ሆኗል።

በዚያም በፍጹም ትሕርምት ሲኖር ባልንጀሮቹ ይጠፉበታል። እነሱን ሊፈልግ ሲሔድ ግን አረማውያን ይዘው አሠሩት፤ አሰቃዩት። መንገድ ላይ ውኃ ጠምቷቸው ሲጨነቁ "ውኃ ባጠጣችሁሳ?" አላቸው። "እንለቅህ ነበር።" አሉት።

ጸልዮ ውኃ አፍልቆ ቢያጠጣቸው "አንተማ ታስፈልጋለህና አንለቅህም።" አሉት። ወስደውም ጸይለም በምትባል ሃገር ለባርነት ሸጡት። በዚያ ሲያሰቃዩት ተአምራትን አድርጐ በክርስቶስ አሳምኗቸዋል።

ወደ ጐረቤት ሃገር ሔዶም ዛፍ ሲያመልኩ አገኛቸው። "ወደ ክርስቶስ ተመለሱ።" አላቸው። "እንቢ" ሲሉት ምሳር (መጥረቢያ) ይዞ ወደ ዱሩ ውስጥ ገብቶ ጸለየና ምሳሩን አነሳ።

"በስመ ሥላሴ እገዝመክሙ" ብሎ ቢቃጣቸው አጋንንት የሠፈሩባቸው አሥር ሺህ ዛፎች ባንዴ ወደቁ። በዚህ ምክንያትም አራት መቶ ሺህ ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል። ወደ ሌላ ሃገር ሒዶም ስቃይን ታግሦ ተአምራትን ሠርቶ ብዙዎችን አሳምኗል። በቅድስና ኑሮም በዚህች ቀን ዐርፏል።

አምላከ ይምርሐ ደጉን መሪ፣ አምላከ ዮሐንስ ቸሩን አስተማሪ ያምጣልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅድስት ሐና ነቢይት <3

"ሐና" ማለት "የእግዚአብሔር ስጦታ" ማለት ነው። እጅግ ከሚታወቁ ሴት ነቢያት አንዷ የሆነችው ቅድስት ሐና ከክርስቶስ ልደት አንድ ሺህ አንድ መቶ ዓመታት በፊት በዚህች ቀን እንደ ተወለደች ይታመናል። ቅድስቲቱ ልጅ በማጣት ተቸግራ ከጐረቤት እስከ ሊቀ ካህናቱ ኤሊ ድረስ ሽሙጥና ስድብን ታግሣ ታላቁን ነቢይ ቅዱስ ሳሙኤልን ወልዳለች።

በሐረገ ትንቢቷም፦
"ኢይጻእ ዐቢይ ነገር እምአፉክሙ እስመ እግዚአብሔር አምላክ ማዕምር ውዕቱ - እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ አምላክ ነውና ከአንደበታችሁ (ጽኑዕ) ነገርን አታውጡ።" ስትል ተናግራለች።
(ሳሙ. ፪፥፫)

አምላከ ቅዱሳን የእስጢፋኖስን ጸጋ፣ የፊልያስን ማስተዋልና የሐናን በጐነት ያሳድርብን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ጥቅምት ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ወቀዳሜ ሰማዕት)
፪.ቅዱስ ፊልያስ ሰማዕት
፫.ቅድስት ሐና ነቢይት
፬.ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ
፭.የደብረ ሊባኖስ ሰማዕታት (ካቶሊካውያን የገደሏቸው)
፮.ቅዱሳን ሔራን ሰማዕታት
፯.አባ ዲዮስቆሮስ ካልዕ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
፪.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፫.አባ ገሪማ ዘመደራ
፬.አባ ጰላሞን ፈላሢ
፭.አባ ለትጹን የዋህ
፮.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆጵሮስ)

"እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።
.....አንዳንዶቹ ተነስተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር። ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም። በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሱ።
.....በሸንጐም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት።"
(ሐዋ ፮፥፰-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለእናታችን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና ለአባ ያቃቱ ሊቀ ጳጳሳት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሰባቱ ኪዳናት <3

"ተካየደ" ማለት "ተስማማ፣ ተማማለ" እንደ ማለት ሲሆን "ኪዳን" በቁሙ "ውል፣ ስምምነት" እንደ ማለት ነው። ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ሰዎችም ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል። ልዩነቱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጓል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ ሰባት እንደ ሆኑ ታስተምራለች። ስለዚህም ዛሬ ፈጣሪ ቢረዳን እነዚህን ሰባት ኪዳናት በጥቂቱ እንመለከታለን።
"ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ"
"ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ።"
(መዝ. ፹፰፥፫)

፩. ኪዳነ አዳም
አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት፣ የፍጡራን አስተዳዳሪ፣ ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ ነው። እግዚአብሔር ከአዳም ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው። ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ።
(ዘፍ. ፫፥፩)
አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን ተስፋ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ኪዳንን ተቀበሉ።
(ቀሌምንጦስ፣ ገላ. ፬፥፬)

፪. ኪዳነ ኖኅ
ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት አሥር ትውልድ ዓለም በዓመፃ ተሞላች። ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች። ከመርከቡ ከወጣ በኋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት ቃል ኪዳን ተጋቡ። "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ" እንዲል።
(ዘፍ. ፱፥፲፪)

፫. ኪዳነ መልከ ጼዴቅ
መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ የክርስቶስም ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው። በአሥራ አምስት ዓመቱ መንኖ አጽመ አዳምን ይዞ በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት ነበር።
እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን አትሞታል። በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን አልቀመሰም። ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል።
(ዘፍ. ፲፬፥፲፯፣ ዕብ. ፯፥፩)

፬. ኪዳነ አብርሃም
ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት፣ ሥርወ ሃይማኖት፣ የጽድቅም አበጋዝ ነው። ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና እግዚአብሔር "በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ።" አለው።
(ዘፍ. ፲፪፥፩)
የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን ሰጠው።
(ዘፍ. ፲፯፥፩-፬)

፭. ኪዳነ ሙሴ
ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ፣ የእሥራኤል እረኛ፣ የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነው። በፈጣሪው ትዕዛዝ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለአርባ ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል።
(ዘጸ. ፳፥፩፣ ፴፩፥፲፰)

፮. ኪዳነ ዳዊት
ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት፣ ጻድቅ፣ የዋህና ቡሩክ የሆነ አባት ነው። እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ።" (መዝ. ፻፴፩፥፲፩) ሲል ምሎለታል። አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ "አልዋሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን።
(መዝ. ፹፰፥፴፭)

፯. ኪዳነ ምሕረት
በብሉይ ኪዳን የነበሩ ስድስቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲኦል ማዳን ግን አልቻሉም። ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ ነበር። ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ።

በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ፣ አድጎ፣ ተጠምቆ፣ አስተምሮ፣ ሙቶ፣ ተነስቶና ዐርጐ ሥጋ ማርያምን በዘባነ ኪሩብ አስቀመጠው። ኪዳነ ምሕረት (የምሕረት ኪዳን) የምንለው አንዱ ታዲያ ይሔው ነው።

የጌታችን መጸነሱ፣ መወለዱ፣ መሰደዱ፣ መጠመቁ፣ ማስተማሩ፣ ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ፣ መሰቀሉ፣ መሞቱና መነሳቱ፣ ማረጉና መንፈስ ቅዱስን መላኩ በአንድ ላይ ኪዳነ ምሕረት ይባላል። ታዲያ ይህ ሁሉ የተደረገው በሥጋ ማርያም ነውና የኪዳኑ ባለቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።

የእርሷ ኪዳን የስድስቱን አበው ኪዳናት ፍጹም በማድረጉ "የኪዳናት ማሕተም" ይባላል። የድንግል ማርያም ኪዳኗ ከሲኦልና ከገሃነም ሊታደገን አቅሙ አለውና። መድኃኒታችን ክርስቶስ ለድንግል እናቱ ቃል ኪዳኑን ያጸናላት ደግሞ ካረገ ከዓመታት በኋላ ጐልጐታ ላይ ነው።

እመ ብርሃን በዚያ ቁማ ስለ ኃጥአን ስታለቅስ "እናቴ ሆይ! በስምሽ ያመነውን በቃል ኪዳንሽ የተማጸነውን እምርልሻለሁ።" ብሎ ደስ አሰኝቷታልና። ይሔው በእመ ብርሃን ምልጃና ቃል ኪዳን ምዕመናን ከመቅሰፍትና ከገሃነመ እሳት ማምለጥ ከጀመሩ ሁለት ሺህ ዓመታት ሆኑ። ዛሬም እኛ ኃጥአን ልጆቿ ከእሳት እንደምታድነን አምነን በጥላዋ ሥር እንኖራለን።

"ኢትዝክሪ ብነ አበሳነ ኃጢአተነ ወጌጋየነ ማርያም እሙ ለእግዚእነ
በኪዳንኪ ወበስደትኪ ድንግል ተማሕጸነ።"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአታችን፣ አበሳችንና በደላችንን አታስቢብን ዘንድ በስደትሽና በኪዳንሽ ተማጽነናል።"

ቸሩ ልጇ ከበረከተ ኪዳኗ አይለየን።

<3 አባ ያቃቱ ሊቀ ጳጳሳት <3

በምድረ ግብጽ ከተነሱና ለመንጋው ከራሩ አበው ጳጳሳት አንዱ አባ ያቃቱ ናቸው። አባ ያቃቱ መጻሕፍትን የተማሩ በገዳምም የኖሩ በመሆናቸው እንደ ቀደምቶቻቸው ቤተ ክርስቲያኗን በቅን መርተዋል።

ፓትርያርክ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ብዙ ጭንቅ ያሳለፉ ሲሆን እግዚአብሔር አቅሎላቸዋል። ከማረፋቸው በፊትም ከእርሳቸው ቀጥለው የሚሾሙትን በጸጋ ተናግረዋል። አባ ያቃቱ ለግብጽ አርባ ዘጠነኛ ሊቀ ጳጳሳት ናቸው።

በረከታቸው ይደርብን።

ጥቅምት ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ያቃቱ ሊቀ ጳጳሳት
፪.ጻድቃን እለ ድርቂ
፫.አባ ጳውሊ ገዳማዊ
፬.አባ ማርቆስ መስተጋድል
፭.አባ አሮን መስተጋድል

ወርኀዊ በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
፬.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮.አባ ዳንኤል ጻድቅ
፯.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)

"የምድር ባለጠጐች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ።
ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብሯ ነው።
ልብሷ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው።
በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ።
.....በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ።
በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ። ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ።"
(መዝ ፵፬፥፲፪-፲፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥቅምት ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ዘሚካኤል (አረጋዊ)
፪.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
፫.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፬.ቅዱስ ሙሴ መርዓዊ
፭.ቅድስት እድና (የአረጋዊ እናት)
፮.አባ ማትያስ (የአረጋዊ ረድዕ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፫.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፬.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

"ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል። ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም።"
(ማቴ ፲፥፵፩-፵፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አባ ዘካርያስ ገዳማዊ <3

ይህ ታላቅ ጻድቅ ባለ ጥዑም ዜና ነው። ወላጆቹ እሱንና አንዲት ሴትን ከወለዱ በኋላ አባቱ መንኖ ገዳም ገባ። ከዘመናት በኋላ ረሃብ በሃገሩ ሲገባ እናቱ ወስዳ ለአባቱ ሰጠችው። ይህን ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።

በገዳም ከአባቱ ጋር ሲኖር ከመልኩ ማማር የተነሳ አባቶች መነኮሳት "ይህ ልጅ ይህን መልክ ይዞ እንዴት መናኝ መሆን ይችላል!" ሲሉ ሰማ። በሌሊትም ተነስቶ በሕፃን አንደበቱ "ጌታዬ! መልኬ ካንተ ፍቅር ከሚለየኝ መልኬን አጠፋዋለሁ።" አለ። ከገዳሙም ጠፋ።

አባትም በጣም አዘነ። ከአርባ ቀናት በኋላ ግን ሊያዩት የሚያሰቅቅ አካሉ ሁሉ የቆሳሰለ አንድ ነዳይ ሕፃን መጥቶ ወደ ገዳሙ ተጠጋ። ይህ ሕፃን በጾም፣ በጸሎትና በትሕትና ተጠምዶ ለአርባ አምስት ዓመታት አገለገለ።

በነዚህ ዓመታት ሁሉ ይህ አካሉ የተለወጠ ሕፃን ቅዱስ ዘካርያስ መሆኑን ያወቀ የለም። እንዲህ የቆሰለውም አሲድነት ካለው የጉድጓድ ውኃ ውስጥ ሰጥሞ ለአርባ ቀናት በመጸለዩ ነው።

በመጨረሻ ግን አባቱ በምልክት ለይቶት አለቀሰ። "ልጄ! አንተ ለእኔ

አባቴ ነህ።" ብሎታል። አበው መነኮሳትም ተሰብስበው እጅ ነስተውታል። በሰባት ዓመቱ የመነነው አባ ዘካርያስ በሃምሳ ሁለት ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል።

አምላከ አፈ ወርቅ ዮሐንስ የድንግል እመ ብርሃንን ፍቅሯንና ውዳሴዋን ይግለጽልን። ከአባቶቻችን ክብርና በረከትንም ያሳትፈን።

ጥቅምት ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፪.አባ ዘካርያስ ገዳማዊ
፫.አባ ማርዳሪ ጻድቅ
፬.ቅዱስ አብጥማዎስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬.ቅዱስ አስከናፍር
፭.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

"እናንተ የምድር ጨው ናችሁ።
.....እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል። በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።"
(ማቴ ፭፥፲፫-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥቅምት ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ (የነገሠበት)
፪.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ
፬.ቅድስት ልዕልተ ወይን
፭.ቅዱስ ሳሙኤል ነቢይ
፮.ጻድቃን ጴጥሮስ ወጳውሎስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፫.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፭.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፮.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

"ከሕዝቤም የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ።
ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት። ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት።
እጄም ትረዳዋለች። ክንዴም ታጸናዋለች።
ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም። የዓመጻ ልጅም መከራ አይጨምርበትም።
ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ። የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ።"
(መዝ ፹፰፥፳-፳፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በፌስቡክ ገጻችንም https://www.facebook.com/ገድለ-ቅዱሳን-Gedle-Kidusan-Acts-of-Saints-179772015557994 ያገኙናል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባ ያዕቆብ ስዱድ እና ለእናታችን ቅድስት ጲላግያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ያዕቆብ ስዱድ <3

'ጳጳስ' ማለት 'አባት - መሪ - እረኛ' ማለት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ሥልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ ሦስት ናቸው። እነሱም ዲቁና፣ ቅስና፣ ጵጵስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ ዘጠኝ ያህል ክፍሎች አላቸው። ከእነዚህም ከፍተኛው ሥልጣን ጵጵስና ነው።

ጵጵስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው። ሥልጣኑ በምድር 'ሸክም ዕዳ' ሲሆን በሰማይ ግን 'ክብር' ነው። ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ጵጵስናን አይመኝም።

ቅዱስ ጳውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ጵጵስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ።" (፩ጢሞ. ፫፥፩) ማለቱን ይዞ 'ሹሙኝ' ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው። ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል። የከፋው ግን የጳጳሱ ነው።

አንድ ጳጳስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም። ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና። ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው።" (ዮሐ. ፲)
ስለዚህም ክህነት/ጵጵስና ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው።

አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የጵጵስና መናብርትን መሥርተው ትምህርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል። ከእነዚህ መንበረ ጵጵስናዎች አራቱ የበላይ ናቸው። እነዚህም የቅዱስ ጴጥሮሱ የሮም፣ የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ፣ የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ጳውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው።

እነዚህ መናብርት ከክርስቶስ ዕርገት እስከ ፬፻፵፫ (፬፻፶፩) ዓ/ም ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል። ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው።

የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ጳጳሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች፤ ታከብራለች።

በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን። እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና። ከእነዚህም መካከል አንዱ አባ ያዕቆብ ሲባሉ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ የአንጾኪያ መንበር ፓትርያርክ ነበሩ።

ቅዱሱ በገዳማዊ ሕይወት የተመሠከረላቸው፣
በትምህርት የበሰሉና ለመንጋው የሚራሩ በመሆናቸው በምዕመናን ይወደዱ ነበር። ነገር ግን ተረፈ አርዮሳውያንና መለካውያን ከነገሥታቱ ጋር አብረው ብዙ አሰቃዩዋቸው። በመጨረሻም ከመንበራቸው አፈናቅለው ወደ በርሃ አሳድደዋቸዋል። ከስደት በኋላም አባ ያዕቆብ በዚህች ቀን ዐርፈዋል።

<3 ቅድስት ጲላግያ ገዳማዊት <3

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚል እግዚአብሔር የኃጥኡን መመለስ እንጂ ሞቱን አይፈልግም። በጠፋው በግ መገኘት ደስ ይለዋል። በእግርህ ሒድ እንኳ አይለውም። ይልቁኑ በትከሻው ተሸክሞ ከጐረቤቶቹ ጋር ደስ ይለዋል እንጂ።

ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ቅዱሳን አንዳንዶቹ ጭንቅ ከሆነ የኃጢአት ሕይወት የተመለሱ ናቸው። ግን ድንቅ በሆነ ንስሐቸው 'ቅዱሳን' ከመባል ደርሰዋል። ከእነዚህም አንዷ ቅድስት ጲላግያ ናት።

ይህቺ ቅድስት እናት በልጅነቷ በመልኳ ምክንያት ስህተት ያገኛት ናት። አምላክ የፈጠረውን መልክና ገላ እንዴት መጠቀም እንዳለብን እየተማርን አይደለምና በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ገላችን ለዲያብሎስ ሰጥተነዋል።

ይህቺ እናትም ችግሯ ይኼው ነበር። ስለ ገጽታዋና ገላዋ የነበራት የተሳሳተ አመለካከት መጀመሪያ ወደ ትውዝፍት (ምንዝር ጌጥ) ቀጥሎም ወደ ዝሙት ከተታት። ለዘመናትም የሰይጣን ወጥመድ ሆና ኑራለች።

ፈጣሪ ግን ለሁላችንም የመዳን ቀን ጥሪ አለውና
እሷንም ጠራት። ምናልባትም በዘመኗ የብዙ ሰባክያንን ትምህርት ሰምታለች። አንዱም ግን ወደ ልቧ አልገባም። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ያላደረበት አስተማሪ በጥሩ አማርኛ ልባችን ደስ ያሰኝ ይሆናል እንጂ ሊለውጠን አይችልም።
በዘመኑም የሚታየው ትልቁ ችግር ይኼው ይመስለኛል። እግዚአብሔር የሾማቸው አባቶቻችን ተቀምጠው ወጣቶች መድረኩን የሙጥኝ ብለነዋል።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ጲላግያ አንድ ቀን የሰማችው የደጉ ጳጳስ ትምህርት ግን ፈጽሞ ዘልቆ ተሰማት፣ ተጸጸተች፣ አለቀሰች። ወደ ጳጳሱ ሔዳ "ማረኝ" አለች፤ ንስሐ ሰጣት። እርሷም ንብረቷን ሁሉ መጽውታ በርሃ ገባች።

አንገቷን ደፍታ በጾምና በጸሎት ሰይጣንን ድል ነሳችው። ከሃገሯ ሶርያ ወደ ቀራንዮ ደርሳ ተመልሳ ለሠላሳ ዓመታት ዘጋች። ተባሕትዎዋን ስትፈጽም በጸጋ እግዚአብሔር ተአምራትን ሠርታ ለኃጥአን መንገድ ጧፍ ሆና አብርታ በዚህች ቀን ዐርፋለች።

አምላከ ቅዱሳን የሚያስተውለውን የንስሐ አእምሮን ያድለን። ከወዳጆቹ በረከትም አያርቀን።

ጥቅምት ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ያዕቆብ (ስደተኛው ሊቀ ጳጳሳት)
፪.ቅድስት ጲላግያ ገዳማዊት
፫.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ አርማሚ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
፫.ብፁዐን ኢያቄምና ሐና
፬.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል። ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ።' ይላቸዋል። እላችኋለሁ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።"
(ሉቃ ፲፭፥፫-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥቅምት ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ (ሰማዕት)
፫.ቅዱስ አትናስዮስ ብፁዕ
፬.ቅዱስ ስምዖን ሰማዕት
፭.ቅዱስ ሊዋርዮስ ሊቀ ጳጳሳት
፮.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፯.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት
፰.አቡነ መዝገበ ሥላሴ ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
፱.አፄ ዳዊት ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (ግማደ መስቀሉን ያመጡ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
፫.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
፬.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
፮.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

"ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ። የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። እንዲሁም ጐበዞች ሆይ! ለሽማግሌዎች ተገዙ። ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና። ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።"
(፩ጴጥ ፭፥፫-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአበው ቅዱሳን አባ አጋቶን ወአባ መጥራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ አጋቶን ባሕታዊ <3

ይህንን ቅዱስ የማያውቅ የቤተ ክርስቲያን ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም። እርሱ ታላቅ ጻድቅ፣ ገዳማዊና የእግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል ዘንድ ለሠላሳ ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል።

ይህንን ቅዱስ ሊቃውንት ሲገልጹት "ክምረ ክምር ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል። ትእግስቱ፣ ደግነቱ፣ አርምሞው፣ ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው። በነበረበት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት ነው።

ታላቁ ገዳማዊ ሰው አባ አጋቶን የታላቁ መቃርዮስ ቅዱስ ልጅ ነው። ገዳመ አስቄጥስ እልፍ አእላፍ ቅዱሳንን ስታፈራ ይህ አባት ቅድሚያውን ይይዛል። ምንም በብዛት የሚታወቀው በአርምሞው (በዝምታው) ቢሆንም ባለ ብዙ ትሩፋት አባት ነው።

የሚገርመው የቀደሙ አባቶቻችን የፈለገውን ያህል መናኝ ቢሆኑም የሰው ጥገኛ መሆንን አይፈልጉም። "ሊሠራ የማይወድ አይብላ።" የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ መሠረት አድርገው ከተጋድሎ በተረፈቻቸው ሰዓት ሥራ ይሠራሉ።

አንዳንዶቹ እንደሚመስላቸው ምናኔ ሥራ መፍታት አይደለምና ሰሌን፣ ዕንቅብ፣ ሠፌድ የመሳሰለውን ይሠራሉ። ታላቁ አባ አጋቶንም በአንደበቱ ድንጋይ ጐርሶ በእግሮቹ ቀጥ ብሎ ቆሞ እንቅቦችን ይሠፋ ነበር።

ለነገሩስ ዛሬ ዛሬ እንኳን ወንዶቹ ሴቶችም ቢሆኑ ይህንን ሙያ እየረሱት ነው። ቅዱሱ ግን ይሰፋና ወደ ገበያ ይወጣል። በጠየቁት ዋጋ ሽጦት አንዲት ቂጣ (ጳኩሲማ) ይገዛል። የተረፈውን ገንዘብ ግን እዚያው ለነዳያን አካፍሎት ይመጣል እንጂ ወደ ገዳሙ አይመልሰውም።

ታዲያ አንድ ቀን እንደልማዱ የሠፋቸውን አምስት እንቅቦች ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሔድ መንገድ ላይ አንድ ነዳይ (የኔ ቢጤ) ወድቆ ያገኛል። እንደ ደረሰም ስመ እግዚአብሔር ጠርቶ ይለምነዋል። አባ አጋቶን ከእንቅቦቹ ውጪ ምንም ነገር አልነበረውምና "እንቅቡን እንካ።" አለው።

ነዳዩ ግን ወይ የሚበላ ካልሆነም ገንዘብ እንደሚፈልግ ይነግረዋል። ወዲያው ደግሞ "የምትሠጠኝ ነገር ከሌለህ ለምን ወደ ገበያ ተሸክመህ አትወስደኝም?" አለው። የነዳዩ አካል እጅግ የቆሳሰለ በመሆኑ እንኳን ሊሸከሙት ሊያዩትም የሚከብድ ነበር።

ጻድቁ ግን ደስ እያለው ያለማመንታት አንስቶ ተሸከመው። ከረጅም መንገድ በኋላም ከገበያ በመድረሳቸው አውርዶ ከጐኑ አስቀመጠው። ያ ነዳይ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ቢለምንም የሚዘከረው አጣ። አባ አጋቶን አንዷን እንቅብ ሲሸጥ "ስጠኝ?" ይለዋል። ጻድቁም ይሠጠዋል።

እንዲህ "ስጠኝ" እያለ የአምስቱንም እንቅቦች ዋጋ ያ ነዳይ ወሰደበት። አባ አጋቶን ግን ምንም ቂጣ ባይገዛ በሆነው ነገር አልተከፋምና ሊሔድ ሲነሳ ነዳዩ "ወደ ቦታዬ ተሸክመህ መልሰኝ?" አለው። አባቶቻችን ትእግስታቸው ጥግ (ዳር) የለውምና ጐንበስ ብሎ በፍቅር አንስቶት አዘለውና ሔደ።

ካነሳበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ይወርድለት ዘንድ ጻድቁ ቆመ። ነዳዩ ግን አልወርድም አለ።
መቼም እኛ ብንሆን ብለን እናስበውና ምን እንደምናደርግ ይታወቃል። ጻድቁ ግን ዝም ብሎ ቆመለት።

ትንሽ ቆይቶ ግን ስለ ለቀቀው ሊያየው ዞር ቢል መሬት ላይ የለም። ቀና ሲል ግን ያየውን ነገር ማመን አልቻለም። ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ። ነዳይ መስሎ እንዲያ ሲፈትነው የነበረው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነበር።

ክንፎቹን ዘርግቶ፣ በብርሃን ተከቦ፣ በግርማ ታየው፤ ከወደቀበትም አነሳው። "ወዳጄ አጋቶን! ፍሬህ፣ ትእግስትህ፣ ደግነትህ ግሩም ነውና ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ።" ብሎት ተሰወረው። ጻድቁም በደስታ ወደ በዓቱ ሔደ። አባ አጋቶን ተረፈ ዘመኑን በአርምሞ ኑሮ ዐርፏል።

<3 ቅዱስ መጥራ አረጋዊ <3

ቅዱሱ የሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያን ሲሆን በትውልድ ግብጻዊ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት ከእውቀት እስከ ሽበት ክርስቶስን ሲያመልክ ኑሯል። ዘመኑ ክርስቲያኖች ስለ ሃይማኖታቸው ከባዱን ዋጋ (ሕይወታቸውን) የሚከፍሉበት ነበር።

በወቅቱ ብርቱ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ቢበዙም ብርቱ መንፈሳዊያን ተዋጊ ክርስቲያኖች ነበሩና ውጊያው ተመጣጣኝ ነበር። ዛሬ ደግሞ ሁሉም በዛለበት ዘመን ላይ ተገኝተናል።

ቅዱስ መጥራ ካረጀ በኋላ ነገሥታቱ "ክርስቶስን ካዱ።" እያሉ መጡ። ቅዱሱ ወሬውን ሲሰማ እጅግ ተገረመ። ምክንያቱም መድኃኔ ዓለምን መካድ ፈጽሞ የሚታሰብ ነገር አይደለምና። ቅዱሱ አረጋዊ ስለ ሁለት ነገር ሰማዕትነትን ፈለገ።

አንደኛ በክርስቶስ ስም መሞት የክብር ክብርን ያስገኛልና ከዚሁ ለመሳተፍ ነው። ሁለተኛው ግን ለወጣቶች አብነት (ምሳሌ) ለመሆን ነበር። መልካም መሪ ባለበት ዘንድ ብዙ ፍሬዎች አይጠፉምና። ቅዱስ መጥራ እንዳሰበው ወደ መኮንኑ ሒዶ በአሕዛብ ፊት ክርስቶስን ሰበከ። ስለዚህ ፈንታም ብዙ አሰቃይተው በዚህች ቀን ከተከታዮቹ ጋር ገድለውታል።

አምላከ ቅዱሳን ትእግስታቸውን ያሳድርብን። ከአባቶቻችንም በረከትን ይክፈለን።

ጥቅምት ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ አጋቶን ባሕታዊ
፪.ቅዱስ መጥራ አረጋዊ (ሰማዕት)
፫.ቅድስት ሶስናና ልጆቿ (ሰማዕታት)
፬.አባ ሖር
፭.ቅድስት በላግያ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
፫.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፬.አቡነ ኪሮስ
፭.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

"ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ። እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።
አቤቱ ለአፌ ጠባቂ አኑር። የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።
ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው። .....ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሠጥ። ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር። ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፤ ይዝለፈኝም።"
(መዝ ፻፵፥፪-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ጥቅምት ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ
፪.ቅዱሳን ኡሲፎርና ኡርያኖስ (ሰማዕታት)
፫.አባ ጰንጠሌዎን ዘጾማዕት
፬.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ (ዕን. ከ፩ - ፫ ያንብቡ።)
፭.ቅድስት ሐና ነቢይት (የሳሙኤል እናት - ፩ሳሙ. ከ፩ - ፪ን ያንብቡ።)
፮.አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ኢትዮጵያዊ (ፍልሠቱ)
፯.ቅዱስ ሄኖስ ነቢይ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፣ በወይን ሐረግም ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሥራ ቢጐድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ በጐች ከበረቱ ቢጠፉ፣ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፣
እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል። በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለሁ።"
(ዕን ፫፥፲፯-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስና ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ ገብረ ሕይወት <3

ጻድቁ የተወለዱት ግብጽ (ንሒሳ አካባቢ) ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ፣ የቅዱሳን የበላይ፣ ተጋድሎአቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው።

የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አንደበት ይኖራል?
እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል?
ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን?

አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ እህል ያልቀመሱ (ምግባቸው ምስጋና ነውና።)፣ ልብስ ያልለበሱ (ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና።)፣ ሐዋርያዊ ሆነው ከግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት፣ ሃገራችንን አስምረው አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ ዐርፈዋል።

ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም፣ ገብረ ሕይወትም ይባላሉ። በአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ወንጌልን ሰብከዋል። በዚህም በሚሊየን (አእላፍ) ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል።

ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል። እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል። ለየት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው። ከእልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና።

የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለመቶ ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው።

ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት። በስምንተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ነው። ፍጥረታትን ሁሉ አዝዘው መጋቢት ፭ ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል።

ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ።
"ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ
ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ
ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ
ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ
ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ።" እንዲል።

የጻድቁ በዓል ጥቅምት ፭ ቀን የሚከበረው ብዙ ጊዜ መጋቢት ፭ ዐቢይ ጾም ውስጥ ስለሚውል ተውላጥ (ቅያሪ) ሆኖ ነው።

<3 ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ <3

ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ የከበረ ሽምግልናውም ያማረ ነው። ብዙዎቻችን የምናውቀው በበዓለ መስቀል ስሙ ተደጋግሞ ሲጠራ ነው። ግን ይህ ታላቅ ሰው ለቅድስት ዕሌኒ መካነ መስቀሉን አሳያት ከሚል አረፍተ ነገር የዘለለ ታሪኩ ሲነገርለት ብዙ ጊዜ አንሰማምና እስኪ በዕለተ ዕረፍቱ ስለ ቅዱሱ ጥቂት እንበል።

ቅዱስ ኪራኮስ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን እናቱ ቅድስት ሐና ትባላለች። በእጅጉ የተባረከች ሴት ናት። ምንም በነገዳቸው አይሁድ ቢሆኑም የዘመኑ የአይሁድ ክፋት አልገዛቸውም። የተባረከች እናቱ ታሪክ እያስጠናች ከማሳደጓ ባለፈ አስቀድማ ኦሪቱን ነቢያቱን እንዲያውቅ አደረገች።

አስከትላም ሕገ ክርስትናን እንዲረዳ አደረገችው። የታሪክና የመጻሕፍት ምሑሩ ቅዱስ ኪራኮስ ከእናቱ ጋር ሆኖ እግዚአብሔርን እያገለገለ ክርስቶስን እያመለከ ቆየ። በዚህ ጊዜ ግን እድሜው እየገፋ ነበር።

ሠለስቱ ምዕት (ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት) ጉባኤያቸውን ከፈጸሙ በኋላ ቅድስት ዕሌኒም መስቀሉን ፍለጋ ስትወጣ ትልቁ ፈተናዋ የተቀበረበትን ቦታ ማወቅ አለመቻሏ ነበር። እንዲያውም አማራጭ ስታጣ በአካባቢው የነበሩ አይሁድን ምሥጢር እንዲያወጡ ቀጥታቸው ነበር። በኋላ ግን ኪራኮስ ስለሚባል ደግ ታሪክ አዋቂ ሰው ሰምታ ተገናኙ።

ቅዱስ ኪራኮስም አባቶቹ አይሁድ ናቸውና አካባቢውን ያውቀው ነበር። ችግሩ ቆሻሻው ተራራ በመሆኑ ከሦስቱ የትኛው እንደ ሆነ አለመታወቁ ነበር። ቅዱሱ ግን ለዚህም መፍትሔ ነበረውና "ደመራ ደምረሽ በእሳት አቃጥለሽ እጣን ጨምሪበትና ይገለጥልሻል።" አላት።

ቅድስት ዕሌኒም የተባለችውን በትክክል ፈጽማ የመድኅን ክርስቶስን ቅዱስ ዕጸ መስቀል አገኘች። ቅድስት ዕሌኒ ወደ ሃገሯ ከተመለሰች በኋላም ቅዱስ ኪራኮስ በኢየሩሳሌም አካባቢ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ።

አረጋዊው ቅዱስ የሚገርም እረኛ ነውና የባዘኑትን ሲፈልግ በቤቱ ያሉትንም ሲያጸና ብዙ ደከመ። በቅርቡ ያሉትን በአፉ የራቁትን ደግሞ በጦማር (በመልእክት) አስተማረ። በወቅቱ በአካባቢው ኤልያኖስ የሚሉት ከሃዲ ንጉሥ ነበርና በቅዱስ ኪራኮስ ላይ ተቆጣ።

ወደ እርሱ አስጠርቶ በአደባባይ ቅዱስ ቃሉን ይጽፍበት የነበረው ቀኝ እጁን አስቆረጠው። ቅዱስ ኪራኮስ ግን እጁ መሬት ላይ ወድቃ ደሙ እየተንጠፈጠፈ ተናገረ፦ "አንተ ልብ የሌለህ ንጉሥ! እጄን ቆርጠህ ከክርስቶስ ፍቅር ልትለየኝ አትችልም።" አለው።

በዚህ የተበሳጨ ንጉሡ እሳት አስነድዶ አልጋውን አግሎ ቅዱሱን ጠበሰው። ኪራኮስ ግን በእሳቱ ላይ ሳለ ወደ እስራኤል ፈጣሪ በዕብራይስጥኛ ጸለየ። በማግስቱ እናቱን ቅድስት ሐናን አምጥተው የነደደ እሳት ውስጥ ጣሏት።

ለሦስት ሰዓት ያህል በእሳት ውስጥ ስትጸልይ ቆይታ በጦር ወግተው ገደሏት። ቅዱስ ኪራኮስንም ለአራዊት ሰጡት። አራዊቱ ሰገዱለት። በሌሎች ዓይነት ስቃዮችም ፈተኑት፤ ግን እንቢ አላቸው። በመጨረሻው በዚህች ቀን ገድለውት የክብርን አክሊል ተቀዳጅቷል።

አምላከ ቅዱሳን በእነርሱ ላይ የበዛች ፍቅሩን ለእኛም ያድለን። ፍሬ ትሩፋት፣ ፍሬ ክብር እንድናፈራም ይርዳን። ክብራቸውንም አያጉድልብን።

ጥቅምት ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ
፪.ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ (ጳጳስ ወሰማዕት)
፫.ቅድስት ሐና ሰማዕት (እናቱ)
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)
፭.አባ ጳውሎስ ሰማዕት (አርዮሳውያን አንቀው የገደሉት አባት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
፬.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
፭.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)

"ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።"
(ገላ ፮፥፲፬-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዲስ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አባ ስምዖን ሊቀ ጳጳሳትና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ <3

ሰማዕቱ የተወለደው በምድረ ግብጽ አሕዛብ (ተንባላት) በሰለጠኑበት የመጀመሪያው ዘመን ነበር። በተለይ ተንባላቱ ግብጽና ሶርያን ከያዙ በኋላ ባልተጠበቀ ፍጥነት በኃይልም በሰውም ተደራጅተው ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ (ልብ በሉልኝ ሊቀ ሰማዕታት አይደለም።) የተወለደው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር።

እናቱ የተመሠከረላት ክርስቲያን ብትሆንም እንዳለመታደል አባቱ ተንባላታዊ (አሕዛብ) ነበር። ስሙንም "መዛሕዝም" ይሉታል። ሕፃኑ እንደተወለደ ያወጡለት ስም አሕዛባዊ ከመሆኑ ባለፈ በሰዓቱ መጠመቅ አልቻለም። የወቅቱ ሕግ ከወላጆቹ አንዱ አሕዛባዊ ከሆነና አጠምቃለሁ ቢባል የሚከተለው ሰይፍ ነበር። በዚህ ምክንያት ሳይጠመቅ ሰባት ዓመት ሞላው።

እናቱ ግን ሕፃን ቢሆንም ፍቅረ ክርስትናን ታስተምረው ነበር። ባይጠመቅም ጠበሉን እምነቱን ትቀባው ነበር። ደብቃ ቅዳሴ ታሰማውም ነበር። አንድ ቀን ግን ሕፃናት ሲቆርቡ አይቶ ካልቆረብኩ ብሎ አለቀሰ። ምን ታድርገው? ወደ ውጪ አውጥታ ከአውሎግያ (የሰንበት በረከት) አበላችው። "ጌታዬ! ልጄን እርዳው?" አለች።
ልክ በአፉ ሲቀምሳት መዓዛ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና ፍጹም ተደሰተ። ትንሽ ከፍ ሲል ለምን እንደማይጠመቅና እንደማይቆርብ እናቱን ጠየቃት። "ልጄ ሆይ! ይገድሉሃል።" አለችው።
ከዚህች ቀን ጀምሮ የሚጠመቅበትን ዘዴ ይፈልግ ጀመር።

አስቀድሞ ትምህርተ ክርስትናን ተማረ። ለአካለ መጠን ሲደርስ አፈላልጐ ጠንካራ ክርስቲያን የሆነች ሴት አገባ። ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ሚስቱን ስለ መጠመቅ አማከራት። "ሌላ ሃገር ሒደህ ተጠመቅ።" አለችው። ከግብጽ ተነስቶ ሶርያ ገባ። አባቶችን አፈላልጎ ተጠመቀ። ቀጥሎም መንገዱን ወደ ልዳ አደረገ።

ወደ ደብሩ ተጠግቶ አባቶችን "ስም አውጡልኝ?" ቢላቸው መንፈስ ቅዱስ አናግሯቸው "ጊዮርጊስ" አሉት። እርሱም ደስ እያለው ባጭር ታጥቆ የልዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገለግለው ገባ። ትንሽ ቆይቶ ሁከት መንፈሳዊ ተሰማው፤ ማለትም ስለ ሃይማኖቱ ደሙን ማፍሰስ ፈለገና ወደ ግብጽ ተመለሰ።

በዚያ ያሉ አሕዛብ በክርስትና ስም፣ ልብስና ሞገስ ሲመለከቱት ተበሳጩ፤ ዕለቱኑ አሠሩት። ሌሊት እናቱና ሚስቱ መጥተው "አደራ! ፍቅረ ዓለም እንዳያታልልህ። ሰማዕት ብትሆን ላንተም ክብር ለእኛም ሞገስ ነው።" ብለው አጽናኑት። እንዲህ ያሉ እናትና ሚስት ማግኘትም ታላቅ እድል ነው።

ሐዲስ ጊዮርጊስም ጸና። ከዚያች ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ደበደቡት፣ አካሉን ቆራረጡት፣ ደሙንም መሬት ላይ አንጠፈጠፉት። በየመንገዱ እየጎተቱ ተሳለቁበት። እርሱ ግን ክርስቶስን ወዷልና ሁሉን ታገሰ። ሌሊት በሆነ ጊዜም ጌታችን ተገልጦ "ከሰማዕታት ተቆጠርህ።" አለው።

በማግስቱ በአደባባይ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት። ክፋታቸው የጸና ነውና ሥጋውን በእሳት አቃጠሉት። ወደ ባሕርም ጣሉት። እናቱ ከባሕር ስታወጣው ግን ምንም አላገኘውም ነበር። በዚህች ቀን እናቱና ሚስቱ በክብር ቀብረውታል።

<3 አባ ስምዖን ሊቀ ጳጳሳት <3

በምድረ ግብጽ ተነስተው በማርቆስ ወንጌላዊ መንበር ላይ ይቀመጡ ዘንድ ከተገባቸው ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ እኒህ አባት ናቸው። ከልጅነታቸው መንነው ብዙ ዘመናትን በተጋድሎ በማሳለፋቸው ሥጋዊ አካላቸው ደካማ ሆኖ ነበር።

ከገዳማዊ አገልግሎታቸው ቀጥሎም ከእርሳቸው በፊት ለነበሩ ሁለት ፓትሪያርኮች ረዳት ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ጊዜም ለመንጋው የሚሆኑ ተግባራትን ከመፈጸማቸው ባሻገር በጾምና በጸሎት መጋደልን አልተውም ነበር።

ጊዜው ደርሶ በእግዚአብሔር ፈቃድ በሕዝቡና ጳጳሳቱ ምርጫ የእስክንድርያ ሃምሳ አንደኛ ፓትርያርክ ሲሆኑ እርሳቸው እንደ ሌሎቹ አበው "አልፈልግም" ብለው ነበር።

ቀደም ሲል እንዳልነው አካላቸው በተጋድሎ የተቀጠቀጠ ነበርና በመንበራቸው ላይ ለብዙ ጊዜ መቆየት አልቻሉም። እግራቸውን በጠና በመታመማቸው ፈጣሪ ነፍሳቸውን እንዲቀበል ለመኑት፤ እርሱም ሰማቸው። ሊቀ ጳጳሳት ሆነው በተሾሙ በመቶ ስልሳ አምስተኛው ቀን (ማለትም በአምስት ወር ከአሥራ አምስት ቀናቸው) በክብር ዐርፈው ተቀብረዋል።

<3 አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (GIYORGIS OF SEGLA) <3

ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅና ጻድቅ የተወለደው ወሎ ጋስጫ ውስጥ በ፲፫፻፶፰ (፲፫፻፶፯) ዓ.ም ነው። ከልጅነቱ ትምህርት አልገባህ ቢለውም በልቡናው ግን ቅንና ታዛዥ ነበር። መምህሩ "ትምህርት አይገባውምና ውሰዱት።" ቢላቸው "የእግዚአብሔር ነውና ያገልግላችሁ።" ብለው መለሱት። መገፋቱን የተመለከተ አባ ጊዮርጊስ እመቤታችንን ከልቡ ይወዳት ነበረና ይማጸናት ገባ።

ቀን ቀን ገዳሙን ሲረዳ፣ እህል ሲፈጭና ሲከካ፣ ላቡንም ሲያፈስ ውሎ ሌሊት ደግሞ ሲጸልይ ያነጋ ነበር። ድንግል እመቤታችን ጸሎቱን ሰምታለችና ቅዱስ ዑራኤልን አስከትላ መጣችለት። በንጹሐት እጆቿ ባርካው ምሥጢርንም ነገረችው። "ወነገረቶ ሐምስተ ቃላተ" እንዲል። ጽዋዐ ልቡናን አጠጥታው ተሠወረችው።

ከዚህች ሰዓት ጀምሮ አባ ጊዮርጊስ ፍጹም ተለወጠ። በጽድቁ ላይ የሊቅነትን ካባ ደረበ። ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተነትናቸው መናፍቃንንም ምላሽ ያሳጣቸው ገባ። የተረጐማቸውና ያተታቸውን ሳይጨምር አርባ አንድ ድርሰቶችን ደረሰ። (መጽሐፈ ሰዓታት፣ መጽሐፈ ምሥጢር፣ አርጋኖን፣ ኆኅተ ብርሃን፣ ውዳሴ መስቀል ወዘተ የእርሱ ድርሰቶች ናቸው።)
ስለ ሃይማኖትም ጠበቃ ነበር። ስለ ቅድስናውና ውለታው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ትጠራዋለች።
፩.ሊቀ ሊቃውንት
፪.በላዔ መጻሕፍት
፫.ዓምደ ሃይማኖት
፬.ዳግማዊ ቄርሎስ
፭.ጠቢብ ወማዕምር

ጻድቁ ሊቅ በተወለደ በስልሳ ዓመቱ በ፲፬፻፲፰ (፲፬፻፲፯) ዓ.ም ዐርፏል። አባ ጊዮርጊስ የተወለደውም ያረፈውም ሐምሌ ፯ ቀን ነው።
ይህች ዕለት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተጸነሰባት ናት።

ቸሩ አምላክ ከሰማዕቱ ጽናትን፣ ትእግስትን፣ ጸጋ በረከትን ይክፈለን። የቅዱሳኑ በረከትም ይደርብን።

ጥቅምት ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ (ሰማዕት)
፪.አባ ስምዖን ሊቀ ጳጳሳት
፫.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፬ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ
፭.ቅድስት ታኦድራ ልዕልት
፮.ቅድስት ታኦፊላ

ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
፬.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭.አቡነ ዜና ማርቆስ
፮.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
፯.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)

"ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ። በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?
.....እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን። ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።"
(፩ቆሮ ፲፥፲፬-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሊቃውንት አባ ሕርያቆስና አባ ሳዊሮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሊቁ አባ ሕርያቆስ <3

ክርስቲያን ሆኖ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ሁሉ ይህንን አባት ያውቀዋል። አባ ሕርያቆስ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ ሲሆን አካባቢው ብህንሳ (ንሒሳ) ይባላል። ይህቺ ቦታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጨምሮ በርካታ ቅዱሳንን ያፈራች ናት።

አባ ሕርያቆስን በዚህ ዘመን ነበረ ብዬ ትክክለኛውን ዓ.ም ለመናገር ይከብደኛል። ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት መረዳት እንደሚቻለው ግን የነበረበት ዘመን አራተኛው ወይ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ሆነ መገመት ይቻላል።

ቅዱሱ በዘመኑ የተለየ ማንነት የነበረው ሰው ነው። ገና ከልጅነቱ እመ ብርሃንን የሚወዳት በመሆኑ ቅን፣ የዋህና ገራገር ነበረ። መቼም እመቤታችንን ይወዳል ሲባል እንደ ዘመኑ በአፍ ብቻ እንዳይመስለን። ቀንና ሌሊት ለፍቅሯ የሚተጋ ማዕበለ ፍቅሯ የሚያማታው ሰው ነበር እንጂ።

የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ስም ሲጠራ ምስጥ ብሎ ልቡናው ይሰወርበት ነበር። ዘወትር የእርሷን ፍቅር ከማሰብ በቀር ሌላ ሥራ አልነበረውም። የልጅነት ጊዜው ሲያልፍም ድንግልንና ቸር ልጇን ያገለግል ዘንድ መነነ።

ዘመኑ ዘመነ ሊቃውንት እንደ መሆኑ ሁሉም ለትምህርት ሲተጉ እርሱ ግን ለጸሎትና ለደግነት ብቻ ነበር የሚተጋው። ከትምህርት ወገንም የሰሞን ጓዞችን፣ አንዳንድ ቅዳሴያትንና የዳዊትን መዝሙር ተምሮ ነበር።

በተለይ ግን የዳዊትን መዝሙር እየጣፈጠው መላልሶ መላልሶ ያመሰግንበት ነበር። ከዳዊት መዝሙር መካከል ደግሞ መዝሙር አርባ አራትን ፈጽሞ ይወዳት ነበር። ይህቺ ጥቅስ የምትጀምረው "ጐስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" ብላ ነው። የውስጧ ምሥጢርም ስለ ድንግል ማርያምና ስለ ክርስቶስ ነው።

አባ ሕርያቆስ ይህቺን መዝሙር በቃሉ አጥንቶ ቁሞም ተቀምጦም፣ ተኝቶም ተነስቶም ያለ ማቋረጥ ይላት ነበር። እየጣፈጠችው "ልቡናዬ በጐ ነገርን አወጣ።" እያለ ይዘምር ነበር። በወቅቱ ታዲያ የብህንሳ ኤጲስ ቆጶስ በማረፉ ምትክ ሲያፈላልጉ መንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስን መረጠ።

ምንም አለመማሩ ቢያሰጋቸውም "በጸሎቱና በደግነቱ ሃገር ይጠብቃል።" ብለው ሾሙት። ነገር ግን ምንም በሥልጣን የበላያቸው ቢሆን ተማርን የሚሉ ሰዎች ይጠሉት ይንቁትም ነበር። እርሱ ግን እንደ ጠሉኝ ልጥላቸው፣ እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር ያገለግል ነበር።

አንድ ቀን ታዲያ መንገድ ይወጣል። በበርሃ ብቻውን እየተራመደ "ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" እያለ እየዘመረ ተመሥጦ ቢመጣበት መንገድ ሳተ። እርሱ በምስጋናው ሲደሰት እግሩ ግን ከገደል ጫፍ ደርሶ ነበር። ገደሉን ልብ አላለውም ነበርና ሳይታወቀው ወደ ገደሉ ውስጥ ተወረወረ።

በዚህ ጊዜ ደንግጦ ቢመለከት እጅግ ጥልቅ በሆነ ገደል ውስጥ ራሱን አገኘው። ነገር ግን አንድም አካሉ አልተነካም፤ ልብሱም አልቆሸሸም። ለራሱ ተገርሞ ዙሪያ ገባውን ሲመለከት እርሱ ቁጭ ያለበት ብርሃንን የተሞላ የልብስ ዘርፍ ነበር።

"እመ ብርሃን!" ብሎ ሲጮህ የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነች እመቤታችን ከፊቱ ቁማ ታየችው። እመ አምላክን በገሃድ ቢያያት እንደ እንቦሳ ዘለለ።
የሚገርመው ደግሞ የተቀመጠበት የድንግል ማርያም የቀሚሷ ዘርፍ ነበር። እመቤታችን አነጋገረችው፤ ባረከችው። ፍቅሯ ቢመስጠው ከሰው ሳይገናኝ ምግብም ሳይበላ እዚያው ገደሉ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል በተመስጦ ቆይቷል።

በኋላ እመ ብርሃን መጥታ ከገደሉ አውጥታ ወደ ሃገሩ መለሰችው። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ፈተና ገጠመው። አንድ ቀን እመቤታችን በተወለደችበት ግንቦት ፩ ቀን ቅዳሴ "ማን ይቀድስ?" ሲባል ሰዎቹ "አባ ሕርያቆስ ይሁን።" አሉ።

እርሱ ግን "እኔ አይቻለኝም፤ እናንተ ሊቃውንት ቀድሱ።" አላቸው። "አይሆንም" ብለው እርሱኑ አስገቡት። ይህንን ያደረጉት ለተንኮል ነበር። ልክ ወንጌል ተነቦ ፍሬ ቅዳሴ ሲመረጥ እርሱ "እግዚእን (የጌታ ቅዳሴን) ልቀድስ?" ቢል እነርሱ "የሚቀደሰው የሊቅ ቅዳሴ ነው።" አሉት።

ይህንን ያሉት እርሱ የሊቃውንቱን ቅዳሴ አያውቅምና በሰው ፊት እንዲዋረድ ነው። እንዲህም ብለው ባለመማሩ ተሳለቁበት። አባ ሕርያቆስ ግን እያዘነ ወደ መንበሩ ዞረ። ድንግልንም "እመቤቴ መናቄን መገፋቴን ተመልከች።" አላት።

ወዲያው ግን ድንግል ማርያም ወርዳ ቀጸበችው (ጠራችው)። በዘርፋፋው ቀሚሷ ላይም ረቂቅ የሆነ ቅዳሴን አሳየችው። ደጉ ሰው ደስ ብሎት "ጐሥዐ ልብየ" ሲል ሁለቱ እግሮቹ ከመሬት ከፍ አሉ። እርሱም "ወአነ አየድእ ቅዳሴሃ ለማርያም" ብሎ እስከ ኃዳፌ ነፍሱ ድረስ አደረሰው።

ሕዝቡና ካህናቱ በሆነው ነገር ሲደነቁ አንዳንዶቹ "ዝም ብሎ ነው የቀባጠረ።" አሉ። ቅዱሱ ግን ቅዳሴ ማርያምን በብራና ጠርዞ በሕዝቡ መካከል ድውይ ፈወሰበት። እሳት ሳያቃጥለው ውኃ ሳይደመስሰው ቀረ።
መጽሐፈ ቅዳሴው ሙትንም አስነስቷል። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ በዘመኑ ቁጥር አንድ ሊቅ ሆነ። ብዙ መጻሕፍትን ሲተረጉም አጠቃላይ ድርሰቶቹም እልፍ (አሥር ሺህ) ናቸው። ሊቁ እንዲህ በንጹሕ ተመላልሶ ዐርፏል። ይህቺ ቀን ለቅዱሱ የልደቱና ዕረፍቱ መታሰቢያ ናት።

<3 ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ <3

ቅዱስ ሳዊሮስ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው። ወቅቱ መለካውያን (ሁለት ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው። ሊቃውንት "አንበሳ" ሲሉ ይጠሩታል።

ቅዱሱ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ብዙ ሆኖላታል። የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል። ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ።

ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ?" አለችው። እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም።" ሲል መለሰላት። አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት።

እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ። መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው። ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጓዘ። እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ።

በምድረ ግብጽም የጵጵስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ፤ አጸና። በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ።

አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት። ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የካቲት ፲፬ ቀን ዐርፏል። ይህቺ ቀን ዕለተ ስደቱ ናት።

አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት የድንግል እመቤታችንን ጣዕሟን ፍቅሯን ያሳድርብን። የአበውን ሃብትና በረከትም አይንሳን።

Читать полностью…
Subscribe to a channel