gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት
፪.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ
፫.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፬.አባ ይስሐቅ ሊቀ ጳጳሳት
፭.ሊቁ አካለ ወልድ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
፪.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
፫.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፬.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ
፭.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

"እውነት እላችኋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል። በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። ደግሞ እላችኋለሁ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።"
(ማቴ ፲፰፥፲፰-፳)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አባ ቅፍሮንያ ጻድቅ <3

ይህ ቅዱስ ሰው በቀደመ ሕይወቱ አረማዊ ነበር። ነገር ግን በውስጡ ቅንነት ተገኝቶበታልና እግዚአብሔር በቸር አጠራሩ ወደ ቤቱ አመጣው። አባቱ አረማዊ በዚያውም ላይ አገረ ገዢ ነበርና ለቅፍሮንያ ይህንኑ እያስተማረ አሳድጐታል።

አንድ ቀን ግን ፈጣሪ ጥሪውን ላከለት። ይኸውም ገና ወጣት ሳለ የገዳም አበው ያዩትና ትንቢት ይናገሩለታል። "ይህ ሰው በጐ ክርስቲያን፣ ምርጥ ዕቃም ይሆናል።" ሲሉት እንኳን ሌሎቹ ለእርሱ ለራሱም ምንም አልመሰለውም ነበር። በዚህ መንገድ (በአረማዊነቱ) ዓመታት አልፈው ቅፍሮንያ የከተማው መኮንን (አገረ ገዢ) ሆነ።

የግብጽ አረማውያን ገዢዎች እንደ ትልቅ ሥራ የሚያዩት አድባራትን ማቃጠል፣ ገዳማትን መመዝበር ነውና እርሱም ለዚሁ ሥራ ተነሳ። ሠራዊትን አስከትቶ በሠረገላው ተጭኖ ወደ አንድ ገዳም ደረሰ። ልክ የገዳሙን መሬት ሲረግጥ ግን በአንዴ ልቡናው ተሰበረ።

ሠራዊቱን ወደ ከተማ አሰናብቶ እርሱ ብቻውን ወደ ገዳሙ ዘለቀ። ወደ አበ ምኔቱም ቀርቦ ሰገደላቸውና እንዲያጠምቁት ተማጸናቸው። እርሳቸውም አስተምረው አጠመቁት። በዚያውም መንኖ መነኮሰ።

ለዘመናትም በጠባቡ መንገድ ተጋድሎ ከጸጋ (ከብቃት) ደረሰ። በአካባቢው ሰውና እንስሳትን የፈጀውን ዘንዶም ባሪያ አድርጐ ለአሥር ዓመታት ገዝቶታል። ከብዙ ተጋድሎ በኋላም በዚህ ቀን ዐርፏል።

አምላከ ቅዱሳን መላእክት እነርሱን ለረድኤት ይላክልን። ከቅዱሳን አበው በረከትም ይክፈለን።

ኅዳር ፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን አራቱ እንስሳ (ኪሩቤል)
፪.ቅዱስ አፍኒን ሊቀ መላእክት
፫.አባ ቅፍሮንያ ጻድቅ
፬.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ንጉሥ (ዘምስለ ቅዱስ መስቀል)
፭.ቅድስት እግዚእ ክብራ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
፫.አቡነ ኪሮስ
፬.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፭.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)

"በዙፋኑም መካከል፣ በዙፋኑም ዙሪያ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሏቸው አራት እንስሶች ነበሩ። ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል። ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል። ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው። አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል። አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሏቸው።"
(ራዕይ ፬፥፮-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ከወርቅና ከብር ይልቅ ሞገሱ የሚበልጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረሱ እኛን ለመርዳት ይምጣ፤ ይመላለስም።"
(ስብሐተ ፍቁር ዘጊዮርጊስ)

እንኳን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ <3

መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው፣ አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰባት ዓመታት ስቃይ በኋላ ተሰይፏል።
ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ፦
ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃያ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሥልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ (ደራጎን) ሲያመልኩ አገኛቸው። እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ፣ አሳምኖ፣ ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ሰባ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር። በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው። እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ።

ከዚያም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ። ሦስት ጊዜ ሙቶ ተነሣ። ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ "የሰማዕታት አለቃቸው"፣ "ፀሐይና የንጋት ኮከብ" በሚል ይጠራል።
"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ።" እንዲል መጽሐፍ።

ከሰባት ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተአምራት ጋር ተሰይፎ ደም፣ ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል። ሰባት አክሊላትም ወርደውለታል።

ይህቺ ዕለት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያል ቅዳሴ ቤቱ ናት። እርሱ በ፫፻፺ዎቹ አካባቢ ሰማዕት ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በዚያው በሃገሩ ደብር አንጸው፣ አጽሙን አፍልሠው በዚህች ቀን ቀድሰዋታል።

ቅዱሱ ሰማዕት ከሰማዕትነቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተአምረኛ ነውና አንዷን እንመልከት። በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ከነበሩ አራዊት (ነገሥታት) መካከል አንዱ የሆነው ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም የአርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን ደም አፍስሶ ነበርና ፈጣሪ ደመ ሰማዕታትን የሚበቀልበት ጊዜ ደረሰ።

በ፫፻፭ ዓ.ም አካባቢ አረመኔው ንጉሥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተአምረኛነት ሰምቶ እንዲያፈርሱት ሠራዊት ላከ። የሠራዊቱ አለቃም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ላይ ተሳለቀ።

ከፊቱ የነበረውን ቀንዲል በሰይፍ እመታለሁ ሲል ግን ቀንዲሉ ተገልብጦ መሐል አናቱን መታው። እንደ እብድ ሆኖ ሞተ። ሠራዊቱም ሰምቶ ወደ ንጉሡ ሸሸ። ይህን ሰምቶ የተበሳጨው ዲዮቅልጢያኖስ ግን ራሱ ሊያፈርሰው ሔደ። ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ሲደርስ ሚካኤልና ገብርኤል ዓይኑን አጠፉት።

እገባለሁ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ መረዋውን (ደወሉን) ለቀቀበት። ራሱን ቢመታው ደነዘዘ። የብዙ ቅዱሳንን ደም የጠጣው ርጉሙ ንጉሥም አብዶ ለሰባት ዓመታት ፍርፋሪ ሲለምን ኑሮ ሰይጣን ከገደል ጫፍ ወርውሮ ገድሎታል።

አምላካችን እግዚአብሔር ከኃያሉ ሰማዕት ጽናትና ትእግስት፣ በረከትም ይክፈለን።

<3 ቅዱስ ጊዮርጊስ እስክንድርያዊ <3

በቤተ ክርስቲያን "ጊዮርጊስ" የሚባሉ ብዙ ቅዱሳን አሉ። ከልዳዊው ቀጥሎም ይህንን ግብጻዊ ሰማዕት እንጠቅሳለን። ስሙ ጊዮርጊስ የተባለውም በታላቁ ሰማዕት አማላጅነት ስለ ተገኘ ነው።

አባቱ ኅዳር ፯ ቀን የሊቀ ሰማዕታትን ቅዳሴ ቤት ሊያከብር ሒዶ ስለተማጸነው የሚስቱ ማኅጸን ተከፍቶለት ልጅ ወልዷል። ስሙንም ጊዮርጊስ ብሎታል። ባደገም ጊዜ እጅግ ብርቱ ክርስቲያን ሆነ።

የግብጻዊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብርታቱ ምንድን ነው ቢሉ፦
ንጹሕ አምልኮቱ ጾም፣ ጸሎቱ፣ በጐ ምጽዋቱ ነው። "ስም ይመርሕ ኀበ ግብር - ስም ወደ ተግባር ይመራል።" እንዲሉ አበው የሰማዕቱን ስም ይዞ እርሱም ይሔው እድል ገጠመው።

በአጋጣሚ ወላጆቹ ሲሞቱ የሚኖረው ከከተማው መኮንን ቤት ነበር። ምክንያቱም የመኮንኑ ሚስት እኅቱ ናትና። ችግሩ ግን መኮንኑ አርማንዮስ ጣዖት አምላኪ፣ በዚያ ላይ ጨካኝ መሆኑ ነው።

አንድ ቀን ግብጻዊ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመኮንኑን ሴት ልጅ ወደ በርሃ ወስዶ የደብረ ቁስቋም መነኮሳትን ዝማሬ አሰማት፤ ክርስትናንም አስተማራት። ይህንን የሰማው መኮንኑ ግን በብስጭት ቅዱስ ጊዮርጊስንና የራሱን ሴት ልጅ በአደባባይ አሰይፏቸዋል። የክብርን አክሊልም ተቀዳጅተዋል።

<3 ቅዱሳን ዘኖቢስና ዘኖብያ <3

እነዚህ ቅዱሳን እናትና ልጅ ናቸው። ዘኖብያ እናቱ ስትሆን ዘኖቢስ ደግሞ ወጣት ልጇ ነው። የቅዱሳኑ ሃገር ደግሞ ተበይስ ትባላለች። በዘመነ ሰማዕታት ድንቅ በሆነ ሕይወታቸውና ተአምራቸው እንደ ኮከብ አብርተዋል። ከአምስት ጊዜ በላይም ከተደገሰላቸው የሞት ወጥመድ በእግዚአብሔር ኃይል አምልጠዋል።

"ክርስትናችንን አንክድም፤ ከክርስቶስ ፍቅር አንለይም በማለታቸው፦
፩.ልብሳቸውን ገፈው፣ በዓየር ላይ ሰቅለው፣ ደማቸው እስኪንጠፈጠፍ ገረፏቸው። በክርስቶስ ኃይል ተረፉ።
፪.የእንጨት መስቀሎችን አሰርተው በአደባባይ ቸንክረው ሰቀሏቸው፤ ከዚህም ዳኑ።
፫.ሁለት ወንበሮች ላይ ችንካሮችን ተክለው በዚያ ላይ አስቀመጧቸው። አሁንም በፈጣሪ ኃይል ዳኑ።
፬.ጥልቅ ጉድጓድ ተቆፍሮ፣ እሳትም ነዶ በዚያ ውስጥ ተጨመሩ። ቅዱስ መልአክ ግን ወርዶ አጠፋላቸው።
፭.አንዴ ደግሞ በቤት (በውሽባ ቤት) እሳት ነዶ በውስጥ ተጨመሩና ተዘጋባቸው። እግዚአብሔር ግን ከዚህም ታደጋቸው። ስለ ክብራቸውም ቅዱስ መልአክ ወርዶ እነርሱን አክብሮ፣ መኮንኑን ዙፋኑን አሸክሞ በአደባባይ አዙሮታል።

አንዴም ጋን አሸክሞ በኋላቸው አስከትሎታል። በእነዚህ ሁሉ ድንቆች ብዙ ሕዝብ እያመነ በሰማዕትነት ሙቷል። በመጨረሻ በዚህች ቀን ዘኖብያና ዘኖቢስ ሲሰየፉ መብረቅ ወርዶ ሃምሳ አራት አሕዛብን ገድሏል። በዚህም መኮንኑ ተገርሞ በክርስቶስ አምኗል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቋም (ሚጠታ ለማርያም)
፪.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፫.ቅድስት ሰሎሜ ቡርክት
፬.ቅዱስ ዮሳ (ወልደ ዮሴፍ)
፭.ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሊቅ
፮.አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ
፯.አባ ፊልክስ ዘሮሜ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፪.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፫.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፬.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፭.አባ አርከ ሥሉስ
፮.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃኑዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። አሕዛብንም ሁሉ በብረት ዘንግ ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ፣ ወንድ ልጅ ወለደች። ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቧት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ሥፍራ ወደ በረሃ ሸሸች።"
(ራዕይ ፲፪፥፬-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

አምላከ ቅዱሳን የቀደምቶቻችንን የዋህነት ለእኛም ያድለን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ታላቁ ቅዱስ ዮሐኒ (ዘትግራይ)
፪.አባ አሞኒ ዘናሕሶ
፫.ቅዱስ ለንጊኖስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት
፭.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪.ቅዱስ ጳውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)
፬.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ

"ወደ ጌታ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም። ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጐኑን በጦር ወጋው። ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ። ያየውም መስክሯል። ምስክሩም እውነት ነው። እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል። ይህ የሆነ 'ከእርሱ አጥንት አይሰበርም።' የሚል የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። ደግሞም ሌላው መጽሐፍ 'የወጉትን ያዩታል።' ይላል።"
(ዮሐ ፲፱፥፴፫-፴፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ይከታተሉን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሰማዕታት ቶማስ፣ ያዕቆብ ወዮሐንስ፣ አቢማኮስ ወአዛርያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቶማስ ዘደማስቆ <3

ቅዱስ ቶማስ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ተወልዶ ያደገ ሶርያዊ ክርስቲያን ነው። ከልጅነቱ እንደሚገባ መጻሕፍትን ተምሮ ለዲቁና፣ ለቅስና ከዚያም ለጵጵስና በቅቷል። በወቅቱ የሶርያ ዋና ከተማ በሆነችው ደማስቆ ላይ ተሹሞ ያገለግልም ነበር።

ታዲያ ዘመኑ በየቦታው ደም የሚፈስበት ነበርና የክርስቶስን መንጋ መጠበቁ ቀላልና የዋዛ ሥራ አልነበረም። በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ያፈሱ የነበሩት ደግሞ ተንባላት (የመሐመድ ተከታዮች) ናቸው። ሰባተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲደርስም ተንባላት ግብጽንና ሶርያን በቁጥጥር ሥር በማድረጋቸው ክርስቲያኖች ተቸገሩ።

በወቅቱም ቅዱስ ቶማስ ሲያስተምር የሰማው አንድ መሐመዳዊ "እንከራከር" አለው። ቅዱሱም ሊቅ ነበርና ስለ መሐመድ ሐሰተኛነት፣ ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ካስረዳው በኋላ ንጹሕና ሰማያዊ ሕግ ቅዱስ ወንጌል እንጂ ቁርዓን እንዳልሆነ ነገረው።

በአደባባይ በመረታቱ ያፈረው መሐመዳዊም በብሽቀት ሒዶ ለደማስቆው ገዢ ከሰሰው። ቅዱስ ቶማስም ተይዞ ቀረበ። "እንዴት እምነታችን እስልምናን ትሳደባለህ?" ቢለው ቅዱሱ "እውነቱን ተናገርኩ እንጂ አልተሳደብኩም።" ሲል መለሰለት።

መኮንኑም "እሺ! ክርስቶስ ማን ነው? ስለ ወንጌልና ቁርዓንስ ምን ትላለህ?" ሲል የተሳለ ሰይፍ አውጥቶ ጠየቀው። የቀናችው እምነት ክርስትና ክብርነቷ በሰማይ ነውና መጨከንን ትጠይቃለች።

ቅዱስ ቶማስ ምንም ሳይፈራ "ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይና የምድር ፈጣሪና አምላክ ነው። ቅዱስ ወንጌል ሰማያዊና የሕይወት ሕግ ሲሆን ቁርዓን ደግሞ የመሐመድ የፈጠራ መጽሐፍ ነው።" ይህንን የሰማው መኮንን በቁጣ አንገቱን እንዲመቱት አዘዘ። ቅዱስ ቶማስም በዚህች ቀን ስለ ቀናች ሃይማኖቱ አንገቱን ሰጠ።

<3 ቅዱሳን ያዕቆብ ወዮሐንስ <3

አሁን ደግሞ ወደ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተመልሰን ወደ ምድረ ፋርስ (ኢራን) ወርደን ቅዱሳንን እናዘክር። እነዚህ ቅዱሳንም በሃገረ ፋርስ (ኢራን) በመንግሥተ ሳቦር ዘመን የነበሩ አበው ናቸው። ሳቦር ማለት ፀሐይንና እሳትን የሚያመልክና እጅግ ጨካኝ የነበረ ንጉሥ ነው።

ቅዱሳኑ ያዕቆብና ዮሐንስ የሐዋርያትን ስም ብቻ ሳይሆን ግብራቸውን፣ ቅድስናቸውንም የያዙ ነበሩ። ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት ባይሆንም ፋርስ ግን በዚህ ዘመንም ለክርስቲያኖች የግፍ ከተማ ነበረች።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ፣ ከቅዱስ መርምሕናም እስከ ቅዱስ ኮቶሎስ ሰማዕትነትን የተቀበሉት በዚህችው ሃገር ውስጥ ነው። ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስም ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን በልኩ ተምረው፣ መጻሕፍትንም ተረድተው ለክህነት ተመርጠዋል።

በኋላም ቤተ ክርስቲያን "ይገባችኋል" ስትል ጳጳሳት አድርጋ ሾመቻቸው፤ እነርሱም አላሳፈሯትም። የክርስቶስን መንጋ እያስተማሩ፣ እየናዘዙ ጠበቁላት። ንጉሡ ሳቦር ግን ሕዝቡን ለፀሐይና ለእሳት ሊያሰግድ ላደረገው ጥረት እንቅፋት ሁነውበታልና ጠላቸው።

በወታደሮቹ አስይዞም በፍርድ አደባባይ አቆማቸው። ሕዝቡን በአዋጅ ጠርቶ አስፈሪ እሳት አስነድዶ "ሕዝቡ ለፀሐይ እንዲሰግድ እዘዙ።" ቢላቸው "እንቢ" አሉት።

ከነ ልብሳቸው አንስተው ወደ እሳቱ ወረወሯቸው። ቅዱሳኑም በመከራው (በነደደው እሳት) መካከል ሆነው ለሕዝቡ ተናገሩ። "አምላክ አንድ እግዚአብሔር ነውና እንዲህ በሃይማኖታችሁ ጽኑ።" አሏቸው። እሳቱም አቃጥሎ ገድሏቸው የክብርን አክሊል ተቀዳጁ።

<3 ቅዱሳን አቢማኮስ ወአዛርያኖስ <3

አሁን ደግሞ ወደ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ዋናው ዘመነ ሰማዕታት እንመለስ። በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩ ቅዱሳን ሰማዕታት ሁለቱ አቢማኮስና አዛርያኖስ ናቸው። አውሬዎቹ መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስ ዓለምን ለሁለት ተካፍለው በክርስቲያኖች ላይ ግፍን ሲሰሩ ሁለቱ ቅዱሳን በሮም ግዛት ሥር ይኖሩ ነበር።

በዘመኑ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ማነጸ፣ መዘመር፣ እምነትን መግለጥ ይቅርና ሲያማትቡ መታየት እንኳ ያስገድል ነበር። ነገሥታቱ የሾሟቸው ተከታዮቻቸው ክርስቲያኖችን ከዋሉበት አላሳድር፣ ካደሩበትም አላውል አሉ።

ታላቅ ግፍ፣ ሰቆቃና ጭንቅ በሆነበት በዚያ ወራት የሞተው ሙቶ እኩሉ ሲሰደድ አቢማኮስና አዛርያኖስ ግን በከተማ መሐል ተረጋግተው ክርስቶስን ያመልኩ ነበር። ይህም ተደርሶባቸው ተከሰሱና ተይዘው ቀረቡ።

መኮንኑ ሁለቱን ክርስቲያን ወጣቶች ሲመለከታቸው ምንም የፍርሃት ምልክት አልተመለከተባቸውምና ተገረመ። "ማንን ታመልካላችሁ?" አላቸው። እነርሱም "የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን!" ሲሉ መለሱለት።

"ክርስቶስን ትክዳላችሁ ወይስ ትሞታላችሁ?" ቢላቸው "ሰነፍ!" ሲሉ በአደባባይ ገሰጹት። "የፈጠረ፣ ያከበረ፣ ሥጋውን ደሙን የሰጠ ጌታ እንዴት ይካዳል?" ሲሉም እቅጩን ነገሩት። በድፍረታቸው የደነገጠው መኮንኑም በዚያች ሰዓት ሞትን አዘዘባቸው። በዚህች ቀንም አንገታቸውን ተሰይፈው ለክብረ ሰማዕት በቅተዋል።

አምላከ ቅዱሳን ሰማዕታት በእነርሱ ያሳደረውን ትእግስትና ጽናት በእኛም ላይ ያሳድርብን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ኅዳር ፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ዘደማስቆ
፪.ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስ
፫.ቅዱሳን አቢማኮስ ወአዛርያኖስ
፬.አባ አበጊዶ ዘትግራይ
፭.ታላቁ አባ ዘካርያስ
፮.ጉባኤ ቅዱሳን ሰማዕታት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
፪.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን።' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።"
(ሮሜ. ፰፥፴፭-፴፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃን አቡነ መድኃኒነ እግዚእ፣ ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል እና ቅዱስ ኪርያቆስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ መድኃኒነ እግዚእ <3

መዘንጋታቸው እጅግ ከሚያስቆጭ ኢትዮጵያውያን አባቶች ትልቁን ሥፍራ እኒህ አባት ይወስዳሉ። የማር ወለላን በሚያስንቅ ጣዕመ ሕይወታቸው ሃገራችንን ያጣፈጡ፣ ብርሃን ሆነው ብዙ ቅዱሳንን የለኮሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው።

አባ መድኃኒነ እግዚእ የተወለዱት በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ትግራይ (አዲግራት) ውስጥ ነው። ወላጆቻቸውም ቀሲስ ሰንበትና ሒሩተ ማርያም ይባላሉ። በደግነትም እጅግ የታወቁ እንደ ነበሩ ገድላቸው ይናገራል። "መድኃኒነ እግዚእ" ማለት "ጌታ መድኃኒታችን ነው።" ማለት ነው።

ብዙ ጊዜም "ዘደብረ በንኮል - ሙራደ ቃል" እየተባሉ ይጠራሉ። "ደብረ በንኮል" ማለት ትግራይ ውስጥ የሚገኝና ጻድቁ በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያነጹት ገዳም ነው። "ሙራደ ቃል" ደግሞ "የቃል (የምሥጢር) መውረጃ" እንደ ማለት ሲሆን በቦታው ሱባኤ የያዘ ሰው ልክ እንደ ቅዱስ ያሬድ ምሥጢር እንደሚገጥለት የሚጠቁም ስም ነው።

ጻድቁ መድኃኒነ እግዚእ በልጅነታቸው ከሊቁ ካህን አባታቸውና ከሌሎችም መምህራን ተምረው ምናኔን መርጠው ገዳም ገብተዋል። በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተግተው ጸጋ እግዚአብሔር ሲሰጣቸው ወደ ደብረ በንኮል ሒደው ገዳም መሠረቱ።

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን (በተለይ ከአሥራ ሦስተኛው እስከ አሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ያለው) የብርሃን ዘመን ይባላል።
ምክንያቱም ዘመኑ
ክርስትና ያበበበት፣
መጻሕፍት የተደረሱበት፣
ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት፣
ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው።

ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ
አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣
አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣
አባ ሰላማ ካልዕ፣
አቡነ ያዕቆብ፣
ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ፣
አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ፣
አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው።

በተጨማሪም
አሥራ ሁለቱ ንቡራነ ዕድ፣
ሰባቱ ከዋክብት፣
አርባ ሰባቱ ከዋክብት፣
አምስቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር። ከእነዚህ መካከልም የሰባቱ እና የአርባ ሰባቱ ከዋክብት አስተማሪ፣ የአበው ሦስቱ ሳሙኤሎች (ዘዋልድባ፣ ዘጣሬጣና ዘቆየጻ)ና የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ።

ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው፣ አስተምረው፣ አመንኩሰው፣ መርቀው ሰደው፣ ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ። ታላቁ ጻድቅና ሰባኬ ወንጌል አባ ዓቢየ እግዚእም (ጐንደር ውስጥ እባብና ጅብ እንዳይጐዳ የገዘቱ አባት ናቸው።) የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ነበሩ ይባላል።

ጻድቁ መድኃኒነ እግዚእ በተትረፈረፈ የቅድስና ሕይወታቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል። አራዊትን ገዝተዋል፣ በአንበሳ ጀርባ ላይ እቃ ጭነዋል። ከረዥም የተጋድሎ ሕይወት በኋላም ኅዳር ፫ ቀን ዐርፈዋል። እድሜአቸውም መቶ ሰማንያ ነው።

"መድኃኒነ እግዚእ አቡነ መስተጋድል
ምንኩስናሁ ምዑዝ ከመ ኮል
በመንፈሰ ጸጋ ክሉል።"
(መጽሐፈ ሰዓታት)

"ተአምረ ኃይልከ አባ መድኃኒነ እግዚእ አቡነ
እም አፈ ዜናዊ ሰማዕነ ወበዓይነ ሥጋ ርኢነ
መንክርኬ አእላፈ ቤትከ ንሕነ
ባሕቱ በዝ ተአምሪከ ርድአነ
ለሰይፈ አርዕድ ንጉሥ ዘወሀብኮ ኪዳነ
ከመ ረድኤቱ ታፍጥን ጊዜ ጸብዕ ኮነ።"
(አርኬ)

<3 ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል <3

የዚህ ቅዱስ ኢትዮጵያዊ ዜና ሕይወት ለሁላችንም ትልቅ ትምህርትነት ያለው ነው። በተለይ በምክንያት ከቅድስና ሕይወት እንዳንርቅ ያግዘናል ብየም ተስፋ አደርጋለሁ። የቅዱሱ ወላጆች ገላውዴዎስና ኤልሳቤጥ ሲባሉ በምድረ ሽዋ በበጐ ምጽዋታቸው የተመሰከረላቸው ነበሩ።

ፈጣሪ ሰጥቷቸው ኅዳር ፰ ቀን (በበዓለ አርባዕቱ እንስሳ) ወልደውታልና "ዓምደ ሚካኤል - የሚካኤል ምሰሶ" ሲሉ ሰይመውታል። ገና በልጅነቱ ብዙዎችን ያስገርም የነበረው ቅዱሱ አንዴ በሦስት ዓመቱ ከቅዳሴ መልስ ጠፋቸው።

ወላጆቹ እያለቀሱ በሁሉ ቦታ ፈለጉት። ግን ሊገኝ አልቻለም። በሦስተኛው ቀን የሞቱን መታሠቢያ ሊያደርጉ ካህናትና ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ግን ባዩት ነገር ተገረሙ። ሕፃኑ ዓምደ ሚካኤል ከቤተ መቅደሱ መሃል ከታቦቱ በታች ካለው መንበር (ከርሠ ሐመር ይሉታል።) ቁጭ ብሎ ይጫወታል።

ያየ ሁሉ "ዕጹብ ዕጹብ" ሲልም አደነቀ። ምክንያቱም በተፈጥሮ ሥርዓት ሕፃን ልጅ ያለ ምግብ ሦስት ቀን መቆየት ስለማይችልና ሕፃኑ በዚያ የቅድስና ሥፍራ ላይ ምንም ሳይጸዳዳ በመገኘቱ ነው።

ብፁዕ ዓምደ ሚካኤል ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየተማረ በጾምና በጸሎት አደገ። በአሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ንጉሥ የነበረው ጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብም ቅዱሱን የሠራዊት አለቃ (ራስ ቢትወደድ) ወይም በዘመኑ አገላለጽ የጦር ሚኒስትር አድርጐ ሾመው።

መቼም እዚህ ቦታ ላይ ተቀምጦ መልካምን መሥራት ልዩ ነገርን ይጠይቃል። በተለይ ደግሞ በዙሪያው የሚከቡትን ተንኮለኞች ድል መንሳቱ ቀላል አልነበረም። ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ግን በዘመነ ሲመቱ እነዚህን ሠራ፦
፩.በጠዋት ተነስቶ ነዳያንን ይሰበስብና ቁርስ፣ ምሳ ያበላቸዋል። ይህም ዕለት ዕለት የማይቋረጥ በመሆኑ ሃብቱ አልቆ ደሃ ሆነ።

፪.ከቀትር በኋላ ዘወትር ቆሞ ያስቀድስና ጠበል ተጠምቆ ይጠጣል። ማታ ብቻ እህልን ይቀምሳል።

፫.ሽፍታ ተነሳ ሲባል ወደ ዱር ወርዶ፣ ጸልዮ፣ ሽፍታውን አሳምኖት ይመጣል እንጂ አይጐዳውም።

፬.ጦርነት በሚመጣ ጊዜ ክተት ሠራዊት ብሎ ይወርዳል። ግን ለምኖ፣ ጸልዮ፣ ታርቆ ይመጣል እንጂ ጥይት እንዲተኮስ አይፈቅድም ነበር።

በዚህ መንገድ በሦስቱ ነገሥታት (በዘርዐ ያዕቆብ፣ በዕደ ማርያምና እስክንድር) ዘመን ሁሉ አካባቢውን ሰላም አደረገው። ዓለም ግን ዓመጸኛ ናትና በአፄ እስክንድር ዘመን (በ፲፬፻፸ዎቹ) በሐሰት ተከሶ ስደት ተፈረደበትና ወደ በርሃ ተጋዘ።

በዚያም ቅዱስ ሚካኤል ሰማያዊ መናን እየመገበው፣ ሥጋ ወደሙን እያቀበለው ኖረ። ትንሽ ቆይቶ ግን የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በንጉሡ አደባባይ ተገደለ። ለሠላሳ ቀናትም በመቃብሩ ላይ የብርሃን ምሰሶ ወረደ በዚህም ንጉሡ በእጅጉ ተጸጸተ።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ <3

ሃገራችን ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ቅድስና ያላቸው ቅዱሳን ባለቤት ናት። በዘመኑ ያለን ወጣቶችም ሆነ ጐልማሶች ከቤተ ክርስቲያንና ከቅድስና ሕይወት ለምን እንደራቅን ስንጠየቅ ከምንደረድራቸው ምክንያቶች አንዱ ሥራችን ነው።

ነገር ግን ሥራው በራሱ ኃጢአት እስካልሆነ ድረስ በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ቢሆን ቅድስናን ማስጠበቅ እንደሚቻል አበው አሳይተውናል። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም ከእነዚህ ቅዱሳን አንዱ ነው።

እርሱ ንጉሥ ነው። ግን ገዳማዊ ሕይወትን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያሳየ ጻድቅ ነው።
ሁሉ በእጁ ነው። እርሱ ግን ንጹሕና ድንግል ነው።
እርሱ የጦር መሪ ነው። ግን በእጁ ደም አልፈሰሰም።
እርሱን "ወደድንህ፣ ሞትንልህ።" የሚሉ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ነበሩት። ለእርሱ ግን ፍቅር ማለት ክርስቶስ ነበር።
የሃገር መሪ፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እንደ መሆኑ እጅግ ባተሌ ነው። ግን ደግሞ ለክርስትናው ጊዜ ያጣ ሰው አልነበረም።

እኛ ቤተ ክርስቲያንን "በሐኪ" ለማለት (ለመሳለም) እንኳ "ጊዜ የለኝም።" ስንል እርሱ ግን አብያተ ክርስቲያናትን ይፈለፍል፣ ያንጽ፣ በክህነቱ ያገለግል፣ ማዕጠንት ያጥን፣ ለረጅም ሰዓትም ይጸልይ ነበር።

እኛ "ሥራ ውያለሁና ደክሞኛል።" ብለን ከስግደት ስንርቅ እርሱ ግን ንጉሥ ሆኖ ሳለ ጦር በፊት፣ በኋላ፣ በቀኝና በግራ ተክሎ ይሰግድ ስለ ነበር ደሙ እንደ ውኃ በምድር ላይ ፈሷል። ይህንን ሁሉ ያደረገው ቅዱሱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ነአኩቶ ለአብ ነው።

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ከነገሡ አሥራ አንድ ነገሥታት አንዱ ሲሆን ከመጨረሻውም ሁለተኛ ነው። እርሱን በአሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም) እና መርኬዛ ናቸው። ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው።

እናቱ መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጆሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር። ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ (ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ) ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች። ሕፃኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ "ነአኩቶ" እያለ ሲዞር ሰማችው።

እዚያው ላይም "ነአኩቶ ለአብ" (አብን እናመስግነው።) ስትል ስም አወጣችለት። ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግሥቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በርሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕፃን ወደ አጐቱ ላሊበላ ቤተ መንግሥት ውስጥ ገባ።

የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከእርሱና ከሚስቱ (ቅድስት መስቀል ክብራ) ሕፃኑ ነአኩቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ። በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና። ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም እድሜው ሠላሳ ደረሰ።

በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ። ቅዱሱ ነአኩቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት። ቤተ መንግሥቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ።

በውስጡም በአራት አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው። ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር፣ ቅዳሴ ሲቀድስ በጾም ይውላል። ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል።

ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል። ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል። እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል። በተለይ ዓርብ ዓርብ ሲሆን ደሙ፣ እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር። እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና።

ከተጋድሎው ጐን ለጐን ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር። በተለይ በ፲፪፻፲፩ ዓ.ም አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት። እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግሥቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት፣ ይቀድስባትም ነበር።

ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ሥውራን ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ። እርሱም "ወገኖቼ! ከወዴት መጣችሁ?" ቢላቸው "መዓዛ እጣንህን አሽተን መጣን።" ሲሉ መለሱለት። በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ "አሽተን (አሸተን) ማርያም" ስትባል ትኖራለች።

ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የነገሠ በሠላሳ ዓመቱ ነው። ለአርባ ዓመታት በእንዲህ ያለ ቅድስና ኑሮ ሰባ ዓመት ሞላው። በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ፤ ሰላምታንም ሰጠው።

"ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለአርባ ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም። ክፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና። የሚያከብርህን አከብረዋለሁ። ደጅህን የሳመውን፣ ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ።" አለው።

ቀጥሎም "ይህች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር።" አለው። እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጠበል ይንጠበጠባል። ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን። ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና።

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደውታል። የተሰወረበትን ዕለት መጽሐፈ ስንክሳር ኅዳር ፩ ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በሦስት ነው ይላሉ። በዙፋኑም ላይ የአጐቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል።

አምላከ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በቃል ኪዳኑ ይማረን። ከበረከቱም አትረፍርፎ ይስጠን።

ኅዳር ፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፪.ቅዱሳን መክሲሞስና ባልንጀሮቹ (ሰማዕታት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
፭.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት

"ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን። ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን።"
(ሮሜ ፮፥፭-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ይከታተሉን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ እና ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

እንዲህ ኃጢአታችን ጽዋዑን ሞልቶ በተረፈበት በዚህ ዘመን አንዲት ሰዓትም ውድ የሆነች የንስሐ ዕድሜ ናት። እግዚአብሔር ግን ደግ ነውና ይሔው ጥቅምትን አስፈጸመን። ባይገባን ነው እንጂ በዚህች ወር ውስጥ ሚሊየኖች በደዌ የአልጋ ቁራኛ ሁነዋል።

ሚሊየኖችም ለንስሐ ሳይበቁ እንዲሁ አንቀላፍተዋል (ሙተዋል)። እስኪ እርሱ አምላካችን ቀሪዋን ዘመን ደግሞ ለንስሐና ለመልካም ሥራ ባርኮ ይስጠን።

<3 ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ <3

በዚህች ዕለት ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነ
¤ወንጌላዊ፣
¤ሐዋርያ፣
¤ሰማዕት፣
¤ዘአንበሳና
¤ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተባለ ቅዱስ ማርቆስ ተወልዷል።

ቅዱስ ማርቆስ እናቱ "ማርያም" አባቱ "አርስጥቦሎስ" ይባላሉ። በልጅነቱ ኦሪትንና የዘመኑን ጥበብ ሥጋዊ በሚገባ ተምሮ ክርስቶስን ከቤተሰቦቹ ጋር ተከትሏል። የመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን ከመቶ ሃያው ቤተሰብ በእድሜ በጣም ትንሹ /ሃያ ዓመት/ እርሱ ነበር።

ለሦስት ዓመታት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ ደክሟል። በተለይ የግብጽና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው። ክህነትን ያገኘን ከእርሱ ነውና።

ቅዱስ ማርቆስ አሥራ ስድስት ምዕራፍ ያለውን ወንጌሉን ሲጽፍ ኪሩብ ገጸ አንበሳ በቀኙ ሊቀ ሐዋርያት በግራው ሆነው ይራዱት ነበር። ቅዱሱ ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ከበርናባስና ጴጥሮስ ጋር ተጉዟል። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ሰሜን አፍሪካ አካባቢ አረማውያን ገድለውታል። ይህቺ ዕለት የልደቱ መታሠቢያ ናት።

ዳግመኛ በዚህች ቀን የቅዱስ ማርቆስን ወላጆችን እናስባቸው ዘንድ ይገባል። ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ) የጌታ ቅን አገልጋይ የነበረ፣
ቅድስት ማርያም (እናቱ) ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ፣ ጌታችንን ያገለገለች፣ ቤቷን ለሐዋርያትና ለጌታ በስጦታ ያበረከተች ቅድስት ናት።

ቤቷም (ጽርሐ ጽዮን) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ይህች ቤት መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል። የእመቤታችን ግንዘትም ተከናውኖባታል።

እግዚአብሔር ከቅዱስ ማርቆስ ቤተሰብ በረከትን ያድለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቁ አቡነ ይምዓታ እና ለአበው ቅዱሳን መርትያኖስ ወመርቆሬዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ይምዓታ ጻድቅ <3

ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮጵያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት። አባ ይምዓታ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው።

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው። በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር፦
፩.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ።
፪.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና
፫.ገዳማዊ ሕይወት ነው።

አባ ይምዓታን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግሥት ነው። እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል። አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል።

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ጰንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ። ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ።

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮጵያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም። ስለዚህም በ፬፻፸ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮጵያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ።

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው። ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው። ይህች ቦታ "ቤተ ቀጢን" ትባላለች።
አባ ይምዓታና ስምንቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር።

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዚያው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ። በወቅቱ በአቡነ ሰላማ፣ በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ ይምዓታ እንደ ገና አቀጣጠሉት።

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት። የካደውን እየመለሱ፣ የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ።

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው። በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ ይምዓታ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማኅበር ነበር። በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም።

የነ አባ ይምዓታ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ። ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው። እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ።
ጰንጠሌዎን በጾማዕት፣
ገሪማ በመደራ፣
ሊቃኖስ በቆናጽል፣
አረጋዊ በዳሞ፣
ጽሕማ በጸድያ፣
ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ።
አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ (እዚያው ትግራይ) ሆነ።

ጻድቁ ወደ ቦታው ሲሔዱ ወንዝ (ባሕር) ተከፍሎላቸዋል። ወደ ቦታው ደርሰውም ገዳም አንጸዋል። በቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠርተው በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል። የአቡነ ይምዓታ ገዳም ገርዓልታ እጅግ ድንቅና ማራኪ ነው።

ነገር ግን ቦታው ድረስ ሒዶ ለማየት ብርታትን ይጠይቃል። በተራሮች መካከል ከመቀመጡ ባሻገር የአባቶቻችንን ጽናት የሚያሳይ ድንቅ ቦታ ነው። ጻድቁ በዚሁ ገዳም ለዘመናት ተጋድለው በዚህች ቀን ዐርፈዋል።

<3 ቅዱሳን መርትያኖስና መርቆሬዎስ <3

እነዚህ ቅዱሳን የቁስጥንጥንያ ሰዎች ሲሆኑ የወቅቱ ፓትርያርክ አባ ጳውሎስም ደቀ መዛሙርት ናቸው። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ በአርዮሳውያን ምክንያት ስደት በሆነ ጊዜ አባ ጳውሎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስና ቅዱስ ሊዋርዮስ ከመንበራቸው ተፈናቀሉ።

በስደቱ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሲያርፍ ቅዱሳኑ አትናቴዎስና ሊዋርዮስ ተመለሱ። አባ ጳውሎስን ግን በእሥር ቤት ውስጥ ሳለ በንጉሡ ትዕዛዝ አርዮሳውያን አንቀው ገደሉት። ይህንን ያወቁት ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ (መርቆሬዎስና መርትያኖስ) ቅዱስ አባታቸውን ቀብረው ንጉሡን ረገሙት።

አርዮሳዊው ታናሹ ቆስጠንጢኖስም ይህንን በሰማ ጊዜ ሁለቱንም አስመጥቶ በአደባባይ በሰይፍ አስመታቸው። ይህ ከተከናወነ ከሃምሳ ዓመታት በኋላም ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ሆኖ በመምጣቱ ሥጋቸውን አፈለሠ። ቤተ ክርስቲያንንም አንጾ ቀድሶላቸዋል።

አምላከ አበው ቅዱሳን በምልጃቸው ይማረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ጥቅምት ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ይምዓታ ጻድቅ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)
፪.ቅዱሳን መርትያኖስ ወመርቆሬዎስ (ሰማዕታት)
፫.አባታችን ያፌት (የኖኅ ልጅ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፭.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
፮.ቅዱስ አባዲርና ቅድስት ኢራኢ

"በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ፤ አትናወጡም። ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት።"
(፩ጴጥ ፫፥፲፫-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ይከታተሉን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አቡነ መብዓ ጽዮን <3

ሃገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ ቅዱሳንን ስታፈራ አንዳንዶቹ ደግሞ የተለዩ ናቸው። ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮን በአሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሽዋ (ሻሞ) አካባቢ የተነሱ ጻድቅ ናቸው። ገና ከልጅነታቸው የእመቤታችንና የጌታችን ፍቅር የሞላባቸው ነበሩ።

በሦስት ዓመታቸው ከእንግዳ የወሰዷት ሥዕለ አድኅኖ ተለይታቸው አታውቅም ነበር። በወጣትነታቸው ጊዜም ብሉያት፣ ሐዲሳትን፣ ቅኔንም ጨምሮ ተምረው ከቤተሰባቸው አስፈቅደው በምናኔ ገዳም ገቡ። ከዚያ በኋላ ያለውን ገድላቸውን ማን ችሎ ይዘረዝረዋል!

በተለይ ዓርብ ዓርብ የጌታን አሥራ ሦስት ሕማማት ለማዘከር ሲቀበሉት የኖሩት መከራ እጅግ ብዙ ነው። ድንጋይ ተሸክመው እንባና ላበታቸው እየተንጠፈጠፈ ይሰግዳሉ። በድንጋይ ደረትና ጀርባቸውን ይደቃሉ፤ ራሳቸውን ይገርፋሉ። በዋንጫ ሐሞት (ኮሶ) ሞልተው ይጠጣሉ።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ወር በገባ በሃያ ሰባት ስለ መድኃኔ ዓለም ጠላ ጠምቀው፣ ንፍሮ ነክረው ወደ ገበያ ይወጡና ይዘክሩ ነበር። ከዝክሩ የነካ ሁሉ ይፈወስ ነበር። ከእንባ ብዛት ዓይናቸው ቢጠፋ ድንግል ማርያም መጥታ ብርሃናዊ ዓይንን ሰጠቻቸው። ስለዚህም "ተክለ ማርያም (በትረ ማርያም)" ይባላሉ።

ጌታችንም ስለ ፍቅራቸው በአምሳለ ሕፃን ይገለጽላቸው፤ እርሳቸውም አቅፈው ይስሙት ነበር። ጻድቁ ተናግረን የማንጨርሰውን ተጋድሎ ተጋድለው ጌታ በዚህች ቀን ነፍሳትን ከሲዖል እንዲያወጡበት ሥልጣንን ሰጣቸው። አባታችን ቅዱሱና ጻድቁ መብዓ ጽዮን ከብዙ ትሩፋት በኋላ ዐርፈዋል።

<3 አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ <3

ጻድቁ አቡነ ጽጌ ድንግል በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቅና ገዳማዊ ናቸው። የዘር ሐረጋቸው ምንም ከቤተ እስራኤል እንደሚመዘዝ ቢታወቅም ኢትዮጵያዊ ናቸው። አስቀድመው አይሁዳዊ በመሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስንና ድንግል እናቱን አያምኑም ነበር።

የተማሩትም ብሉይ ኪዳንን ብቻ ነበር። በጊዜውም "ክርስቶስ አልተወለደም። ትክክለኛው እምነት ይሁዲ ነው።" እያሉ ከክርስቲያኖች ጋር ይከራከሩ ነበሩ። አንድ ቀን ግን ከታላቁ ሊቅና ገዳማዊ አቡነ ዜና ማርቆስ ጋር ተገናኙ።

ጻድቁን ስላልቻሏቸው ተሸንፈው በክርስቶስ አመኑ። አቡነ ዜና ማርቆስም አስተምረው ክርስትና ሲያነሷቸው (ሲያጠምቋቸው) "ጽጌ ድንግል" አሏቸው። ሲመነኩሱም "ጽጌ ብርሃን" ተብለዋል። ቀጥለውም በጾምና በጸሎት ሲጋደሉ፣ እመቤታችንንም ሲለምኑ ምሥጢር ተገለጠላቸው።

የእመ ብርሃንን ሥዕለ አድኅኖ በአበባ ተከባ፣ በብርሃንም ተውጣ ተመለከቱ። በዚህ ምክንያትም ዛሬ በጣፋጭነቱ የሚታወቀውን ማኅሌተ ጽጌን መቶ ሃምሳ አርኬ አድርገው ደረሱ። እስከ ዕለተ ዕረፍታቸውም እመቤታችንና ልጇን በገዳማቸው (ወለቃ አካባቢ የሚገኝ) ሲያመሰግኑ ኑረዋል። በዚህች ቀንም ዐርፈዋል።

አምላከ ቅዱሳን በአማኑኤል ስሙ፣ በማርያም እሙ፣ በፈሰሰ ደሙ፣ በተወጋ ጐኑ፣ በንጹሐን ቅዱሳኑ ይማረን። ከመስቀሉና ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን።

ጥቅምት ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
፪.ቅዱስ መቃርስ ብፁዓዊ
፫.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
፬.አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፪.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፫.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፬.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፭.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

"በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ። ሕማማችንንም ተሸክሟል። እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቆጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ። ስለ በደላችንም ደቀቀ። የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ። በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።"
(ኢሳ ፶፫፥፬-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ይከታተሉን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እና ቅዱስ ጢሞና ሐዋርያ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ <3

ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል ትልቅ ሞገስ የነበረውና "የጌታችን ወንድም" ተብሎ የተጠራ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ የሞተችው እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች። በቤት ውስጥም ስምዖን፣ ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ የምትባል እኅትም ነበረችው።

እናቱ ማርያም ከሞተች በኋላ ዕጓለ - ማውታ (ድሃ አደግ) ሆኖ ነበር። ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ ቤተሰብ ተቀየረ። የበረከት፣ የምሕረትና የሰላም እመቤት የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው።

እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ አለቀሰች። የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው ቆሽሸው ነበር። በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ ያሳዝን ነበር። እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም። ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውኃ አምጥታ የሕፃኑን ገላ አጠበችው። (በአምላክ እናት የታጠበ ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል።)

እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለዘጠኝ ወራት ከተወለደ በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ሕፃኑን ያዕቆብን ተንከባከበችው። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ግን ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ። ከስደት መልስ ግን ለሃያ አምስት ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ ትዝ ብላው አታውቅም። አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና።

ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና ወተትን) ብቻ ነው። ስለዚህም፦
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል መጽሐፍ።
(መልክዐ ስዕል)

ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል።
ለዚህም ምክንያቱ
፩.ለሠላሳ ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፣
፪.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእኅት ልጅ በመሆኑ፣
፫.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች በመሆናቸው፣
፬.ጌታችን ከትኅትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን "ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው። (ሥጋቸውን ተዋሕዶ ተገኝቷልና።)

ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ።" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ገልጧል።
(ያዕ. ፩፥፩)
ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው።
¤ከሰባ ሁለቱ አርድእት ተቆጠረ።
¤ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ።
¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም።" ብሎ ማክፈልን አስተማረ።
¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ።
¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ አገለገለ።
¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ።
¤ሙታንን አስንስቶ፣ ድውያንን ፈውሶ፣ የመካኖችን ማኅጸን ከፍቶ፣ አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተአምራትን ሠራ። እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ መልካሙን ገድል ተጋደለ።

በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ ነው?" ሲሉ ጠየቁት። እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው፤ የእኔም ወንድሜ ነው።" እንዲላቸው ጠብቀው ነበር። (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት)

በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ። "ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦
አምላክ፣
ወልደ አምላክ፣
ወልደ አብ፣
ወልደ ማርያም፣
ሥግው ቃል፣ እግዚአብሔር ነው። እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት ወንድሙ አይደለሁም።" አላቸው።

ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት። በገድል የተቀጠቀጠ አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት። አንዱ ግን ከእንጨት የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ መታው። ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ። ሰማዕቱ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሐምሌ ፲፰ ቀን ሔደ።

ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር። በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ፣ ጸጉሩን ተላጭቶ፣ ገላውን ታጥቦና ልብሱን ቀይሮ አያውቅም።
"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ" እንዲል።

ከጾም፣ ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ አላራምድህ ብሎት ነበር። ስለዚህም አበው "ጻድቁ (ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን። በምልጃውም ምሕረትን ይላክልን።

<3 ቅዱስ ጢሞና ሐዋርያ <3

ቅዱሱ ሐዋርያ ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእትና ከሰባቱ ዲያቆናት ነው። በሐዲስ ኪዳን ስማቸው ከተጠቀሰ ሐዋርያትም አንዱ እርሱ ነው።
(ሐዋ. ፮፥፮)
በትውፊት ትምህርት እንደ ተማርነው ቅዱስ ጢሞና ጌታችንን የተከተለው በመዋዕለ ስብከቱ ነው።

በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል (፲፥፩) ላይ እንደ ተጠቀሰው "ወፈነዎሙ በበክልኤቱ" እንዲል ሁለት ሁለት አድርጐ ሲልካቸው ቅዱስ ጢሞና አንዱ ነበር። በሔዱበትም በስሙ አጋንንት ተገዝተውላቸው፣ ድውያንም ተፈውሰውላቸው ደስ ብሏቸዋል። ጌታችን ግን "አጋንንት ስለ ተገዙላችሁ ደስ አይበላችሁ። ይልቁንስ ስማችሁ በመንግስተ ሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።" ብሏቸዋል።
(ሉቃ. ፲፥፲፯)

ቅዱስ ጢሞና ጌታችንን እስከ ሕማሙ አገልግሎ፣ የጌታን ትንሣኤ ተመልክቶ፣ በዕርገቱ ተባርኮ፣ በበዓለ ሃምሳም ቅዱስ መንፈሱን ተቀብሎ ከፍጹምነት ደርሷል። በመጀመሪያው ዘመንም ሐዋርያት አበው ለአገልግሎት ሰባቱን ዲያቆናት ሲመርጡ እርሱን መንፈስ ቅዱስ አብሮ መርጦታል።
(ሐዋ. ፮፥፭)

በቅዱስ እስጢፋኖስ ሥር ሆኖም እንደሚገባ አገልግሏል። ከቅዱስ እስጢፋኖስ መገደል በኋላም እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት በዓለም ወንጌልን ሲሰብክ ኑሮ በዚህች ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል።

ከበረከቱ ያድለን።

ጥቅምት ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዮሴፍ)
፪.ቅዱስ ጢሞና ሐዋርያ ወዲያቆን
፫.ቅዱስ አግናጥዮስ
፬.ቅዱስ ፊልጶስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት። ትዕግስትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።"
(ያዕ ፩፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ይከታተሉን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአቡነ አቢብ፣ አባ ዕብሎይ እና ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ አቢብ (አባ ቡላ) <3

ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን!
እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን፣ ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ ተሰኝተናል!
ቅዱሱ አባታችን "ቡላ - የእግዚአብሔር አገልጋይ" ብለን እንጠራሃለን።
ዳግመኛም "አቢብ - የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን።

እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን።
አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ!
ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን የተቀበለ!
ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን የሚያወርስ!
የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር፣ ምስጋናና ስግደት በጸጋ ይገባሃል እንላለን።

ልደት
አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት። ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ። ልጅ ግን አልነበራቸውም። ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ።

በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች። ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል።
"ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን"

ጥምቀት
ቅዱሱ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለአንድ ዓመት ቆየ። ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር። እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ 'አጥምቀው' አለችው።

ወደ በርሃ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕፃኑ ተነስቶ እጆቹን ዘርግቶ "አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ። ከሰማይም ሕብስትና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ጳጳሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው። የሕፃኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን።" ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው። እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ።

ሰማዕትነት
የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለአሥር ዓመታት አሳድገውት ድንገት ኅዳር ፯ ቀን ተከታትለው ዐረፉ። ሕፃኑን የማሳደግ ኃላፊነትን የአካባቢው ሰዎች ሆነ። ሕፃኑ ቡላ ምንም የአሥር ዓመት ሕፃን ቢሆንም ያለ ማቋረጥ ሲጾም ሲጸልይ ክፉ መኮንን "ለጣዖት ስገዱ።" እያለ መጣ።

በዚህ ጊዜ በሕፃን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ። በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት። በጅራፍ ገረፉት፣ በዘንግ ደበደቡት፣ ቆዳውን ገፈፉት፣ በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት። ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ሁለት ጊዜ ከሞት ተነሳ። በመጨረሻ ግን ሚያዝያ ፲፰ ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል።

ገዳማዊ ሕይወት
ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው። ከሰማዕታትም ጋር ደመረው። በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ። መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል?" ሲል ጌታን ለመነ።

ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል። ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ።" አለው። ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ ልብሰ መነኮሳትን አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው።

ተጋድሎ
አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዓርብ ዓርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ። ራሱን ይገርፋል፤ ፊቱን በጥፊ ይመታል፤ ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል፤ ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል።

በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል። ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል። ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለአርባ ሁለት ዓመታት ጹሟል። ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር።

የሚታየውም እንደ ተወለደ፣ እንደ ተጠመቀ፣ እንደ ተሰቀለ፣ እንደ ተነሳ፣ እንዳረገ እየሆነ ነበር። አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም። አንተም የብዙዎች አባት ነህና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን።" አለው።
"እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ
ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ
ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል።

ዕረፍት
አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ
መዛሙርትን አፈራ። ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተጨዋወተ ዘለቀ። በተጋድሎ ሕይወቱም ከአሥር ጊዜ በላይ ሙቶ ተነስቷል። በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ።

ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ። አቅም ቢያጣ 'አምላከ አቢብ ማረኝ።' ብሎ ሦስት ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን በስምህ እንኳ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ።" ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ፤ በሰማይም ዕልልታ ተደረገ።

<3 ታላቁ አባ ዕብሎይ <3

ይህ ቅዱስ የአቡነ አቢብ ደቀ መዝሙር ሲሆን በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳንም ቀዳሚው ነው። ብዙ መጻሕፍት 'ርዕሰ ገዳማውያን' ይሉታል። የቅዱሱ ተጋድሎ እጅግ ሰፊ በመሆኑ በዕለተ ዕረፍቱ (የካቲት ፫ ቀን) እንመለከተዋለንና የዚያ ሰው ይበለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! በአፌ ብቻ ሣይሆን ከልቤ እወድሃለሁና ሰላም እልሃለሁ።
ስለዚህ አባት ሆይ! ምስጋናዬን አታቃልብኝ ተቀብለህ ዋጋዬን አሰጠኝ እንጅ። ለእኔ የድሃው ንጹሕ ወርቄ አንተ ጊዮርጊስ ነህና።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአበው ቅዱሳን ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት ዓመታዊ የጉባኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጉባኤ ኒቅያ <3

በዚህች ዕለት (ኅዳር ፱ ቀን) በሃገረ ኒቅያ በእመቤታችን እና በአምላክ ልጇ የሚያምኑ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ተሰብስበዋል።

የሊብያው ሰው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ስምንት ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ።

ጥሪው የተላለፈው በወርኀ ሚያዝያ ሲሆን በመንገድ ችግር ሁሉም ተጠቃለው ኒቅያ የገቡት መስከረም ፳፩ ቀን ነበር። ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና፣ ምግባራቸው የጸና ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ።

እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን። ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው።

እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ፣ ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው። እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና በመገለጫ እንመልከት፦
፩.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (በዘመነ ሰማዕታት ለሃያ ሁለት ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ፣ እግር፣ ጆሮ፣ ከንፈርና ቅንድብ ነው።)
፪.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ (ስለ ቀናች እምነት ለሃምሳ ዓመታት የተጋደለና ለአሥራ አምስት ዓመታት በስደት የኖረ ነው።)
፫.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው።)
፬.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ (በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ፣ ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው።)
፭.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ (ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጓድ ውስጥ ለአሥራ አምስት ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው።)
፮.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ (ከሕፃንነቱ የተቀደሰ፣ በበርሃ የተጋደለ፣ በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው።)
፯.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ፣ ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ፣ በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው።)
፰.ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ (ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ፣ ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው።)
፱.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ (ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው።)

ለአብነት እንዲሆኑን እነዚህን አነሳን እንጂ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱም ሊቃውንት ስለ ቤተ ክርስቲያን ተግተው የተጋደሉ፣ ብዙ ዋጋም የከፈሉ አባቶች ናቸው።

በወቅቱ ታዲያ ቤተ ክርስቲያንን የበጠበጡ ብዙ መናፍቃን ቢኖሩም የአርዮስ ግን ከመጠኑ አለፈ። የእርሱ ኑፋቄ (ፈጣሪያችንን ፍጡር ነው ማለቱ) መነሻው ከእርሱ በፊት ነው። መናፍቃን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ መኖራቸው ግልጽ ነው።

በተለይ ደግሞ ቢጽ ሐሳውያንና ግኖስቲኮች የወለዷቸው እሾሆች አባቶቻችንን እንቅልፍ ነስተው ነበር። የሚገርመኝ በዘመኑ እንደ ነበሩ መናፍቃን ኃይለኝነት የእኞቹ ከዋክብት ሊቃውንት ባይኖሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያሳስብ ነበር።

ግን እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሚገባ ያዘጋጃልና አበው ብርቱ መናፍቃንን በብርቱ መንፈሳዊ ክንድ እያደቀቁ ከጐዳና አስወገዷቸው። የዛሬውን ደካማ ትውልድ ደግሞ የአርዮስ ልጆች ሁለት (ሦስት) ጥቅስ ይዘው ሲያደናብሩት ይውላሉ።

ሐረገ መናፍቃን በርጉም ሳምሳጢ ጳውሎስ፣ በመርቅያንና በማኒ ይጀምራል። በእርግጥ አርጌንስ እና የግብጹ ቀሌምንጦስም ተቀላቅለዋቸዋል። ርጉም ሳምሳጢ ድያድርስን በኑፋቄ ወልዶታል። ድያድርስ ሉቅያኖስን፣ ሉቅያኖስ ደግሞ አርዮስን ወልደዋል።

ይህ አርዮስ እጅግ ተንኮለኛ በመሆኑ ልክ እንደ ዘመኑ መሰሎቹ ግጥምና ዜማ እየጻፈ በየመንገዱ እያደለ በየቤቱ እየሰበከ ብዙዎችን በኑፋቄው በከለ። በመጀመሪያ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ (አስተማሪው) መከረው። ባይሰማው ከአንዴም ሁለት ጊዜ አወገዘው።

ቆይቶ ሰነፉ ጳጳስ አኪላስ ቢፈታውም ሊቁ ቅዱስ እለእስክንድሮስ እንደ ገና አወገዘው። እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት!) ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው።

ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ (ኢሳ. ፱፥፮ ፣ መዝ. ፵፮፥፭ ፤ ፸፯፥፷፭ ፣ ዘካ. ፲፬፥፬ ፣ ዮሐ. ፩፥፩ ፤ ፲፥፴ ራዕይ. ፩፥፰ ፣ ሮሜ. ፱፥፭) አርዮስና የዛሬ መሰሎቹ አንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል።

በወቅቱም በመወገዙ "ተበደልኩ" ብሎ የጮኸው አርዮስ ከሁለቱ አውሳብዮሶች ባልንጀሮቹ (ዘቂሣርያና ዘኒቆምድያ) ጋር ሆኖ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ። ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውንት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ።

ከሚያዝያ ፳፩ እስከ መስከረም ፳፩ ተጠቃለው ገቡ። በ፫፻፳፭ ዓ/ም (በእኛው በ፫፻፲፰ ዓ/ም) ለአርባ ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ። ሱባኤውን ሲጨርሱም በአራቱ ፓትርያርኮች (እለእስክንድሮስ፣ ሶል ጴጥሮስ፣ ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ) መሪነት፣ በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት፣ በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ።

በጉባኤው ሙሉ ሥልጣን በሰማይ ከፈጣሪ፣ በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት። ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ፣ ሥግው ቃል፣ ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት። በጉባኤው መጨረሻም፦
፩.አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ።
፪.ጸሎተ ሃይማኖትን "ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።" እስከሚለው ድረስ ተናገሩ።
፫.ፍትሐ ነገሥትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ብለው አዘጋጁ።
፬.ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ።
፭.በስማቸው የሚጠራ አንድ ቅዳሴን ደረሱ።

ይህ ሁሉ ሲሆን መድኃኒታችን ክርስቶስ ሦስት መቶ አሥራ ዘጠነኛ ሆኖና ገሊላዊ ጳጳስን መስሎ ሁሉን አከናውኖላቸዋል። አባቶችም ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል።

በየዘመኑም ዐርፈው ለክብረ መንግሥተ ሰማያት በቅተዋል።
እኛም እነሆ "አባቶቻችን፣ መምህሮቻችን፣ መሠረቶቻችን፣ ብርሃኖቻችን፣ ምሰሶዎቻችን" እያልን እናከብራቸዋለን።

አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ኪሩቤል (ዐርባዕቱ እንስሳ)፣ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ወአባ ቅፍሮንያ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ዐርባዕቱ እንስሳ <3

እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል።

መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ።
፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።)
፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ)
፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ)
፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል)
፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል)
፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል)
፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል)
፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል)
፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል)
፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው።

ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው።
አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው።
መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው።

መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው።

ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ።

ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ።
ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ።
(ዘካ. ፩፥፲፪)
ምሥጢርን ይገልጣሉ።
(ዳን. ፱፥፳፩)
ይረዳሉ።
(ኢያ. ፭፥፲፫)
እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ።
(መዝ. ፺፥፲፩)
ያድናሉ።
(መዝ. ፴፫፥፯)
ስግደት ይገባቸዋል።
(መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰)
በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ።
(ማቴ. ፳፭፥፴፩)
በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ።

ከእነዚህ ቅዱሳን መላእክት መካከል ደግሞ ትልቁን ሥፍራ ዛሬ የምናከብራቸው ነገደ ኪሩቤል (ዐርባዕቱ እንስሳ) ይይዛሉ። መንፈሳውያን ከመሆናቸው በላይ መንበረ ጸባኦትን እንዲሸከሙ ስላደላቸው ክብራቸው ታላቅ ነው። ከመላእክት ወገንም ቅሩባን እነርሱ ናቸው።

ዘወትርም ስለ ፍጥረታት (ሰዎች፣ እንስሳት፣ አራዊትና አዕዋፍ) ምሕረትን ይለምናሉ። ለዚህም ነው በአራት እንስሳት (በሰው፣ በንስር፣ በላምና በአንበሳ) መልክ የተሳሉት። ቅዱስ መጽሐፍም ስለ እነርሱ ብዙ ይላል።
(ሕዝ. ፩፥፭ ፣ ራዕ. ፬፥፮ ፣ ኢሳ. ፮፥፩)

በተለይ ግርማቸው እንደሚያስፈራ ተጽፏል። "ምሉዓነ ዐዕይንት - ዓይንን የተሞሉ" ይላቸዋል። ይህንንም መተርጉማን "ምሥጢር አዋቂነታቸውንና ግርማቸውን ያጠይቃል።" ሲሉ ተርጉመውታል።

ዐርባዕቱ እንስሳን አራት ሆነው በሥዕል ብናያቸውም "ከመ ርዕየተ እለ ቄጥሩ" እንዲል እያንዳንዱ ከወገብ በላይ አራት በመሆናቸው ተሸካሚዎቹ አሥራ ስድስት መልክ አላቸው። በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን፣ በሁለቱ እግራቸውን ሸፍነው በሁለት ክንፋቸው ይበራሉ። ይህም ብዙ ምሥጢር ሲኖረው ዋናው ግን አርአያ ትእምርተ መስቀል ነው።

"አራቱ" እንስሳ (ኪሩቤል) በሐዲስ ኪዳንም ልዩ ክብር አላቸው። አራቱ ወንጌል ሲጻፍ እየተራዱ ስላጻፉ በስማቸው ተሰይሟል። ቅዱስ ማቴዎስን ገጸ ሰብእ፣ ቅዱስ ማርቆስን ገጸ አንበሳ፣ ቅዱስ ሉቃስን ገጸ ላሕም፣ ቅዱስ ዮሐንስን ገጸ ንስር እየተራዱ ስላጻፏቸው እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ "ዘብእሲ ማቴዎስ"፣ "ዘአንበሳ ማርቆስ"፣ "ዘላሕም ሉቃስ" እና "ዘንስር ዮሐንስ" እየተባሉ ይጠራሉ።

እነዚህ ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ስለ መራዳታቸውም በብዙ ገድላትና ድርሳናት ላይ ተጽፏል። የራሳቸውን "ድርሳነ ዐርባዕቱ እንስሳን" ጨምሮ በገድለ አባ መቃርስና በገድለ አባ ብስንድዮስ ላይ በስፋት ግብራቸው ተጽፏል።

እኛም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ክብራቸውን፣ ረድኤታቸውንና ምልጃቸውን አምነን ዘወትር እናከብራቸዋለን። አባቶቻችን እንዲህ እያሉ እንደ ጸለዩ፦
"ሰላም ለክሙ ኪሩባውያን አፍራሱ
ለመሐይምን ወጻድቅ እንተ ወርቅ አክሊለ ርዕሱ
ኀበ ዝ አምላክ ለእለ ትጸውርዎ በአትሮንሱ
ለእለ ጌገዩ ወለእለሂ አበሱ
ሰአሉ መድኃኒተ ወምሕረተ ኅሡ።"
(አርኬ)

<3 ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ <3

ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያህል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም። ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒና ከአረማዊ አባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ።

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ ጊዜ) ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር። ክርስቲያኖችን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በተደረገው የአርባ ዓመታት ዘመቻ አብያተ መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ። ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ። ሚሊየኖች በግፍ አለቁ።

የዚህን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆንጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም። ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ ቀርነ ሃይማኖት የቆመው፣ ብዙ ሥርዓት የተሠራው፣ ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና።

ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት፣ ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል። በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኑራለት በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ ዐርፏል።

ይህቺ ቀን ታላቁ ንጉሥ በፈለገ ኮቦር ቅዱስ መስቀልን የተመለከተባት ናት። መክስምያኖስን ሊወጋ ወደ ሮም በተጓዘ ጊዜ በሰማይ ላይ መድኅን መስቀል ተዘርግቶ በላዩ ላይ "ኒኮስጣጣን" የሚል በዮናኒ ልሳን ተጽፎበት ተመልክቷል።

ይህንንም "በዚህ ጠላትህን ድል ታደርጋለህ።" ማለት ነው ብለው ተርጉመውለታል። እርሱም በጋሻው፣ በጦሩ፣ በሰይፉና በፈረሱ ላይ የመስቀል ምልክትን አድርጐ ማኅደረ ሰይጣን መክስምያኖስን ድል ነስቶታል። እኛንም በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 አባ ሚናስ ዘተመይ <3

ይህ ቅዱስ አባት ደግሞ ጣዕመ ሕይወቱ ድንቅ ነው። ክርስቲያን ወላጆቹ በሥርዓት አሳድገው በተክሊል አጋቡት። ወደ ሙሽራይቱ ገብቶም "እኅቴ! ይህ ዓለም ኃላፊ ነውና ለምን በድንግልና አንኖርም?" አላት።

እርሷም በደስታ "ይሁን" አለችው። ለበርካታ ዓመታትም ቀን ቀን ሥራቸውን ሲሠሩ፣ እንግዳ ሲቀበሉ ይውላሉ። ሌሊት ደግሞ ወገባቸውን ታጥቀው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ያድራሉ።

ከዓመታት የቅድስና ሕይወት በኋላም ቅዱስ ሚናስ ሚስቱን አስፈቅዶ በርሃ ገብቷል። በተጋድሎ ሳለም እግዚአብሔር ለእረኝነት መርጦት ተመይ በምትባል የግብጽ አውራጃ ላይ ጵጵስናን ተሹሟል። በዚያም እስካረጀ ድረስ ተጋድሎ በዚህች ቀን ዐርፏል።

እንደ ደመና የከበቡን የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አምላክ በቸርነቱ ይማረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት (ቅዳሴ ቤቱ)
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ እስክንድርያዊ
፫.ቅዱሳን ዘኖቢስና ዘኖብያ (ሰማዕታት)
፭.ቅዱስ ሚናስ ዘተመይ
፮.ቅዱሳን መርቆሬዎስና ዮሐንስ (ጻድቃን ወሰማዕት)
፮.አባ ናሕርው ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

"የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፤ ተፈተኑ። በመጋዝ ተሰነጠቁ። በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ፣ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ፣ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።"
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

“ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ እምዕንቈ ባሕርይ ዘየሐቱ
ዘተጽሕፈ ብኪ ትእምርተ ስሙ ወተዝካረ ሞቱ
አክሊለ ጽጌ ማርያም ለጊዮርጊስ ቀጸላ መንግሥቱ
አንቲ ኲሎ ታሰግዲ ሎቱ
ወለኪኒ ይሰግድ ውእቱ”

(የስሙና የሞቱ መታሰቢያ ባንቺ የተጻፈብሽ የሚያበራ ከሆነ ዕንቈ ባሕርይ ይልቅ የጠራ ወርቅ ክበብ ያለው የራስ ቊር የተባለ የጊዮርጊስ የመንግሥቱ የራስ ልብስ ጌጥ ሽልማት የአበባ አክሊል ማርያም ሆይ አንቺ ለእርሱ ሁሉን ታሰግጅለታለሽ (ታንበረክኪለታለሽ) እርሱ ግን ላንቺ ይሰግዳል።)
(አባ ጽጌ ድንግል)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለድንግል እመቤታችን ዓመታዊ የሚጠት በዓል (በዓለ ደብረ ቁስቋም) በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 በዓለ ደብረ ቁስቋም <3

የአርያም ንግሥት፣ የፍጥረታት ሁሉ እመቤት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ልጇን አዝላ ወደ ምድረ ግብጽ ወርዳለች። በወንጌል ላይ (ማቴ. ፪፥፩-፲፰) እንደተጻፈው ጌታችን በተወለደ በሁለት ዓመቱ የጥበብ ሰዎች (ሰብአ ሰገል) ወደ ቤተ ልሔም መጥተው ሰግደውለት ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤውን ገበሩ፤ አገቡለት።

ንጉሥ ተወልዷል መባሉን የሰማ ሄሮድስ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትን ሲፈጅ በቅዱስ ገብርኤል ትዕዛዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አንድ አምላክ ልጇን አዝላ በአንዲት አህያ ጥቂት ስንቅ ቋጥራ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ስደት ወጣች።

ከገሊላ ተነስታ በጭንቅ፣ በመከራ፣ በረሃብና በጥም፣ በሐዘንና በድካም፣ በላበትና በእንባ ተጉዛ ምድረ ግብጽ ገብታለች።
የአምላክ እናቱ እሳትን አዝላ በብርድ ተንገላታለች።
ለእኛ የሕይወት እንጀራን ተሸክማ እርሷ ተራበች።
የሕይወትን ውኃ ተሸክማ ተጠማች።
የሕይወት ልብስን ተሸክማ ተራቆተች።
የሕይወት ፍስሐን ተሸክማ አዘነች።

እመ አምላክ
ተራበች፣
ተጠማች፣
ታረዘች፣
ደከመች፣
አዘነች፣
አለቀሰች፣
እግሯ ደማ፣
ተንገላታች።
ለሚገባው ይህ ሁሉ የተደረገው ለእኛ ድኅነት ነው። በእውነት ይህንን እያወቀ ለድንግል ማርያም ክብር የማይሰጥ ሰይጣን ብቻ ነው። አራዊት፣ ዕፅዋትና ድንጋዮች እንኳ ለአምላክ እናት ክብር ይሰጣሉ።

አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ ደግሞ የክብር ክብር ይገባቸዋል። ከአምላክ እናት ከድንግል ማርያምና ከቸር ልጇ ጋር መከራ መቀበልን መርጠዋልና።

"መድኃኔ ዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ?
ለምን ስደቱን ወደ ግብጽና ኢትዮጵያ አደረገ?"
፩.ትንቢቱን ይፈጽም ዘንድ። በፈጣን ደመና ወደ ግብጽ እንደሚወርድ ተነግሯልና።
(ኢሳ. ፲፱፥፩ ፣ ዕን. ፫፥፯)
፪.ምሳሌውን ለመፈጸም። የሥጋ አባቶቹ እነ አብርሃም፣ ያዕቆብ (እስራኤል)፣ ኤርምያስ ወደዚያው ተሰደዋልና።
፫.ከግብጽ ጣዖት አምልኮን ያጠፋ ዘንድ።
(ኢሳ. ፲፱፥፩)
፬.የግብጽና የኢትዮጵያ ገዳማትን ይቀድስ ዘንድ።
፭.ሰው መሆኑ በአማን እንጂ ምትሐት እንዳልሆነ ለማጠየቅ። (ሰው ባይሆን ኑሮ አይሰደድም ነበር። ሄሮድስ ቢያገኘው ደግሞ ሊገድለው አይችልም። ያለ ፈቃዱና ያለ ዕለተ ዓርብ ደሙ አይፈስምና።)
፮.ስደትን ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠትና
፯.የአዳምን ስደት በስደቱ ለመካስ ነው።

እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር (ለአርባ ሁለት ወራት) በስደት የቆየችባቸው ቦታዎች አሉ። ድንግል ማርያም ከርጉም ሄሮድስ ስትሸሽ መጀመሪያ የሔደችው ከገሊላ ወደ ሶርያ ድንበር (ደብረ ሊባኖስ) ነው።

በዚያ የሸሸጋት ቅዱስ ጊጋር መስፍኑ በሄሮድስ ሲገደል ወደ ምድረ ግብጽ ወረደች። በግብጽም ለብዙ ጊዜ ከአንዱ ወደ ሌላው ስትሸሽ ቆየች።
"እንዘ ከመ በግዕት ግድፍት አመ ሳኮይኪ ውስተ ምድረ በዳ" እንዲል።
(እሴብሕ ጸጋኪ)

ቀጥላም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ገብታ ደብረ ቢዘን ላይ (አሁን ኤርትራ ውስጥ ነው።) ዐረፈች። ከደብረ ቢዘን በደብረ ዳሞ፣ አክሱም፣ ደብር ዓባይ፣ ዋልድባ አድርጋ እየባረከች ጣና ደርሳለች። በጣና ገዳማትም በተለይ በጣና ቂርቆስ ለመቶ ቀናት ቆይታ ቀጥታ በጐጃም ወደ ሽዋ ሒዳ ደብረ ሊባኖስን ቀድሳለች።

ቀጥላም እስከ ደብረ ወገግና ደብረ ሐዘሎ ደርሳለች። በእግሯ ያልደረሰችባቸውን የሃገራችን ክፍሎች በደመና ተጭና ዐይታ ባርካቸዋለች።
ከልጇም በአሥራትነት ተቀብላለች። ሄሮድስ መሞቱን መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የነገራትም እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ትውፊት ያሳያል።

እመ ብርሃንም ከሃገራችን ሰዎች (ከሰብአ ኦፌር) የተቀበለችውን ስንቅና ስጦታ በአምስት ግመሎች ጭና ከቅዱሳኑ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር በዚህች ቀን ደብረ ቁስቋም ውስጥ ገብተው ከድካም ዐርፈዋል፤ ሐሴትንም አድርገዋል።

ዳግመኛም ከክርስቶስ ስደት አራት መቶ ዓመታት በኋላ በዚህች ቀን የግብጿ ደብረ ቁስቋም ታንጻ ተቀድሳለች። የቅዱሳን ማደሪያም ሁናለች።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፫፻፺ዎቹ አካባቢ ድንግል እናቱን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ አእላፍ መላእክትን፣ ጻድቃንንና ሰማዕታትን አስከትሎ ወረደ።

የወቅቱ የግብጽ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎፍሎስና ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ቤተ ክርስቲያኑን አንጸው ሕዝቡን ሰብስበው ይጠብቁት ነበርና ወርዶ ቀድሶላቸው ታላቅ ደስታ ሁኗል።

ስደቷን መሳተፍን ሽተው አበው፦
"እመ ኀሎኩ በጐይዮቱ ውእተ መዋዕለ
እምተመነይኩ ኪያሁ በዘባንየ ሐዚለ
ወበልሳንየ እልሐስ ዘአእጋሪሁ ጸበለ
ወከመ አዕርፍ ምስሌሁ በትረ ዮሴፍ ኀበ ተተክለ
ለወልደ ማርያም በሐጸ ፍቅሩ ልቡናየ ቆስለ።" እንዳሉ።
(ሰቆቃወ ድንግል)
እኛም እመ ብርሃንን ልንሻት ያስፈልገናል።

ይህ ቀን ለእኛ ለክርስቲያኖች ሁሉ እጅግ የደስታ ቀን ነውና ሐሴትን እናድርግ። የሰማይና የምድር ጌታ ለእኛ ሲል ካደረገው ስደቱ በዚህች ቀን ተመልሷልና። ስደቷን አስበን ካዘንን፣ መመለሷን አስበን ደስ ልንሰኝ ይገባልና።
"አብርሒ አብርሒ ናዝሬት ሃገሩ
ንጉሥኪ በጽሐ ዘምስለ ማርያም መጾሩ።" ልንልም ይገባል።

<3 አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ <3

ጻድቁ አቡነ ጽጌ ድንግል በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቅና ገዳማዊ ናቸው። የዘር ሐረጋቸው ምንም ከቤተ እስራኤል እንደሚመዘዝ ቢታወቅም ኢትዮጵያዊ ናቸው። አስቀድመው አይሁዳዊ በመሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስንና ድንግል እናቱን አያምኑም ነበር።

የተማሩትም ብሉይ ኪዳንን ብቻ ነበር። በጊዜውም "ክርስቶስ አልተወለደም። ትክክለኛው እምነት ይሁዲ ነው።" እያሉ ከክርስቲያኖች ጋር ይከራከሩ ነበሩ። አንድ ቀን ግን ከታላቁ ሊቅና ገዳማዊ አቡነ ዜና ማርቆስ ጋር ተገናኙ።

ጻድቁን ስላልቻሏቸው ተሸንፈው በክርስቶስ አመኑ። አቡነ ዜና ማርቆስም አስተምረው ክርስትና ሲያነሷቸው (ሲያጠምቋቸው) "ጽጌ ድንግል" አሏቸው። ሲመነኩሱም "ጽጌ ብርሃን" ተብለዋል። ቀጥለውም በጾምና በጸሎት ሲጋደሉ፣ እመቤታችንንም ሲለምኑ ምሥጢር ተገለጠላቸው።

የእመ ብርሃንን ሥዕለ አድኅኖ በአበባ ተከባ፣ በብርሃንም ተውጣ ተመለከቱ። በዚህ ምክንያትም ዛሬ በጣፋጭነቱ የሚታወቀውን ማኅሌተ ጽጌን መቶ ሃምሳ አርኬ አድርግው ደረሱ። እስከ ዕለተ ዕረፍታቸውም እመቤታችንና ልጇን በገዳማቸው (ወለቃ አካባቢ የሚገኝ) ሲያመሰግኑ ኑረዋል። ጻድቁ ያረፉት ጥቅምት ፳፯ ሲሆን ዛሬ የቃል ኪዳን በዓላቸው ነው።

ቸሩ መድኃኔ ዓለም የድንግል እናቱን ስደት አስቦ ከመንግሥተ ሰማያት ስደት ይሠውረን። ከስደቱ በረከትም ያድለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ጻድቅ አባ ዮሐኒ እና ቅዱስ ለንጊኖስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ አባ ዮሐኒ <3

በምድረ ኢትዮጵያ ዝናቸው ከወጣና ቀደምት ከሚባሉ ጻድቃን አንዱ ቅዱስ አባ ዮሐኒ ("ኒ" ጠብቆ ይነበብ) ነው። አበው ሊቃውንት የቅዱሱን ታሪክና ገድል ገና በልጅነት ስለ ነገሩን አንረሳውም። እጅግ ጣፋጭ ዜና ሕይወት ያለው አባት ነውና።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሃገራችን ቅዱስ አፄ ካሌብ ነግሦ ሳለ አንድ ቅዱስ ሰው ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጡ። እኒህ ሰው "አሞኒ ዘናሕሶ" ይባላሉ። ቅዱሱ ዓለምን ላለማየት ቃል ገብተው በትግራይ በርሃ ይጋደሉ ነበር።

በዘመኑ አፄ ካሌብ የናግራን (የመን) ክርስቲያኖችን ለመታደግ ዘመቻ አድርጎ ነበር። ታዲያ አንድ የንጉሡ ወታደር ወደ ዘመቻ ሲሔድ ሚስቱን ይጠብቅለት ዘንድ ትንሽ ወንድሙን አደራ ይለዋል። ወንድሙ ግን አደራውን ትቶ የትልቅ ወንድሙን ሚስት አስገድዶ ይደርስባትና ትጸንሳለች።

ከዘመቻ የተመለሱት ከአንድ ዓመት በኋላ ነውና ሚስቱን ምጥ ላይ ያገኛት ወታደር ደነገጠ፤ ተቆጣ። የጸነሰችው ከእርሱ እንዳልሆነ ያውቃልና ምጥ ላይ ሆና ሊያዝንላት አልፈለገም።

ለገልጋይ አስቸግሮ ሚስቱን ይደበድባት ገባ። በዚህ ምጥ፣ በዚህ ዱላ ነፍሷን ከሥጋዋ ሊለየው የደረሰችው ያቺ ሴት ግን "ወንድማማችን አላጋድልም።" ብላ ቻለችው። በዚህ ጊዜ ቅዱስ መልአክ ያን ግብጻዊ ባሕታዊ (አባ አሞኒን) አምጥቶ ከሰዎቹ በር ላይ አቆመው።

"ከእርሱ ነው በይ።" አላት። እርሷም "ከዚያ ባሕታዊ ነው።" ብላ ተናገረች። ወታደሩ ባሏም በቁጣ ወጥቶ ቅዱስ አሞኒን በዱላ ስብርብር እስኪል ድረስ ደበደበው። ልጁ ልክ ሲወለድም ከእናቱ ነጥቆ ለባሕታዊው አሳቅፎ አባረረው።

ቅዱስ አሞኒም ሕፃኑን አቅፎ ወደ ተምቤን በርሃ አካባቢ ወሰደው። ግን ምን ምግብ፣ ምን ልብስ፣ ምን መኝታ እንደሚሰጠው ጨንቆት ጻድቁ አለቀሰ። በዚህ ጊዜም ቅዱስ መልአክ የጸጋ ምንጣፍን አነጠፈለት።

ጆፌ አሞራ መጥቶ ክንፉን ሲያለብሰው አጋዘን መጥታ ጡት አጠባችው። በዚህ የተደነቀው ቅዱስ አሞኒ ሕፃኑን "ዮሐኒ" ሲል ስም አወጣለት። ትርጉሙም "ወልደ አራዊት - ወላጆችህ (አሳዳጊዎችህ) አራዊት ናቸው።" እንደ ማለት ነው።

ሕፃኑ ዮሐኒ በዚህ መንገድ ከአሞኒና ከአራዊቱ ጋር አደገ። አምስት ዓመት በሞላው ጊዜም ትምሕርተ ሃይማኖትን፣ የቅድስና ሕይወትን ተማረ። ልክ እንደ መንፈሳዊ አባቱ በጾምና በጸሎት ተወሰነ። ግን እርሱ ከእርሱ፣ ከአሞኒና ከአራዊቱ በቀር ሌላ ፍጥረት፣ ዓለም (ብዙ ሰዎች) መኖራቸውን አያውቅም።

አሥራ ሁለት ዓመት በሞላው ጊዜ ግን ክህነት ይገባዋል ብሎ መንፈስ ቅዱስ ስላሳሰባቸው ቅዱሱ አሞኒ ዮሐኒን ወደ ጳጳሱ ወሰዱት። መንገድ ላይም ቅዱስ ዮሐኒ ወጣት ሴቶች ተሰብሰበው ሲጫወቱ ተመልክቶ "አባ! እነዚህ ጸጉራቸው የረዘመ ደረታቸው ወደ ፊት የወጣ ፍጥረቶች ምንድን ናቸው?" ሲል ጠየቀ።

አባ አሞኒም "ልጄ! እነዚህ ሴቶች ናቸው። ግን ለእንደ እኔና አንተ ያሉ የበርሃ ሰዎች አይሆኑምና አትቅረባቸው።" አለው። ቅዱስ ዮሐኒ መልሶ "አባቴ! ድንገት ቢመጡብኝ ምን ላድርግ?" ሲል ጠየቀ። አባ አሞኒም "ልጄ! ከዘላለም ርስት ከምትነቀል ሩጠህ ብታመልጥ ይሻላል።" አለው።

ከስድስት ዓመታት በኋላ (ዮሐኒ አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላው ማለት ነው።) ቅዱስ አሞኒ ኅዳር ፭ ቀን ዐረፈ። ለአሥራ አራት ዓመታትም ቅዱስ ዮሐኒ ከአራዊትና አባ አበይዶን ከመሰሉ አባቶች ጋር ኖረ። ከንጽሕናው የተነሳም ቅዱሳን መላእክት ያነጋግሩት ነበር።

ስም አጠራሩ በምድረ ትግራይ ሲወጣ ወላጅ እናቱ በሕይወት ነበረችና ሰማች። የአካባቢዋን ሴቶች ሰብስባም ልትገናኘው ወዳለበት ተራራ ገሰገሰች። ወደ ተራራው ደርሳ ስትጠራው ቅዱሱ ተመለከታት።

ወዲያው ትዝ ያለው አባቱ ቅዱስ አሞኒ "ሴት ስታይ ሩጥ።" ያለው ነውና እግሩን አንስቶ ሮጠ። እናቱ ስትከተለው እርሱ ሲሮጥ ከገደሉ ጫፍ ደረሰ። ወደ ኋላ ሲመለከት ሊደርሱበት ነው።

በስመ ሥላሴ ፊቱን አማትቦ ወደ ገደሉ ተወረወረ። በዚህ ጊዜ ግን መንፈሳዊ ክንፍ ተሰጥቶት ተሰወረ። ቅዱስ መልአክም ብሔረ ሕያዋን አስገብቶታል።
ይህንን ታሪክ ሲያደንቁ አበው እንዲህ ብለዋል።
"ሰላም ዕብል ለዘኮነ ሱቱፈ
ምስለ እለ ገብሩ ሰብእ ብሔረ ሕያዋን ምዕራፈ
እምሥርዓተ መላእክት ዮሐኒ ምንትኒ ኢያትረፈ
ከመ ሕይወቶሙ ሕይወተ ተጸገወ ዘልፈ
ወከመ ክንፎሙ አብቆለ አክናፈ።"
(አርኬ)

<3 ቅዱስ ለንጊኖስ ሰማዕት <3

ለንጊኖስ ማለት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከት ዘመን የጲላጦስ ወታደር የነበረ ሰው ነው። ስለ ጌታችን ተአምራት በየጊዜው ይሰማ ነበር። ሔዶ እንዳያገኘው ግን አይሁድን ይፈራ ነበር። እነርሱ "በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ከምኩራብ ይባረር።" ብለው ነበርና።
(ዮሐ. ፱፥፳፪)

ጌታችን በተሰቀለባት ዕለተ ዓርብ ግን ጭንቅ ሆነበት። ጌታን እንዲሰቅሉ ከታዘዙ ወታደሮች እንደ አንዱ ተመርጦ ነበርና በዘዴ አሞኛል ብሎ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ቆየ። በኋላ ግን አይሁድ "በክርስቶስ ሞት ያልተባበረ ሁሉ ወንጀለኛ ነው።" የሚል አዋጅ በማስነገራቸው እየፈራ ወደ ቀራንዮ ሲደርስ "ጐኑን ውጋው።" ብለው ረዥምና ጥቁር ጦር ሰጡት። ለንጊኖስ ወደ ጌታችን ዓይን ተመለከተ። እያየው እንዳልሆነ ገመተ።

ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በባሕርይ ሥልጣኑ ለይቷልና ጦሩን ጨብጦ ወደ ጌታ ጐን ልኮ ወጋው። ከጌታ ቀኝ ጐንም በ"ለ" አምሳል ትኩስ ደምና ውኃ ፈሰሰ። አንዷ ፍንጣቂ ሔዳ የታወረች ዓይኑ ላይ ዐርፋ ዓይኑን አበራች።

ለለንጊኖስ ታላቅ ደስታ ሆነ። ለእኛ ግን ማየ ገቦና ደመ ገቦ ፈለቀልን። የጌታችን ትእግስቱና ቸርነቱ ግን ይደንቃል።
"ከመ ኢየሐስብ ቦቱ ዘኩናተ እዱ ርግዘቶ
በኃጣውኢሁ ለዘኢፈቀደ ሞቶ
ምሕረቶ እሴብሕ ወዐዲ ትዕግስቶ።" እንዳሉ ሊቃውንት።

ጌታችን ከተነሣ በኋላ ለንጊኖስ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘንድ ሒዶ ስለ እውነት፣ ስለ ሃይማኖትም ተማረ። ተጠምቆ ምድራዊ ወታደርነቱን ትቶ እየሰበከ ከኢየሩሳሌም ወደ ቀጰዶቅያ ወረደ። ለዘመናትም ጌታችን ክርስቶስን በሥርዓተ ወንጌል አገለገለ።

በመጨረሻ በጢባርዮስ ቄሣር ዘመን አይሁድ አሳደዱት፤ አንገላቱት። የእነርሱ ወገን ስለነበረም መከራ አጸኑበት። የጽድቅ አርበኛና የክርስቶስ ሐዋርያ ቅዱስ ለንጊኖስ ግን ጸና። አይሁድም አንገቱን ቆርጠውት ለሰማዕትነት በቃ። ቅዱሱ በሕይወቱም በዕረፍቱም ተአምራትን ሠርቷል።

ይህች ዕለት አስተርዮተ ርዕሱ ትባላለች። እርሱን ከገደሉ በኋላ አይሁድ ራሱን ወደ ኢየሩሳሌም ወስደው ጥለዋት ነበር። የእርሱን ሰማዕትነት ያየች አንዲት ክርስቲያንም ከለቅሶ ብዛት ዓይኗ ቢጠፋ ሕፃን ልጇን ይዛ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች።

ወዲያው ግን ሕፃን ልጇ ሞተባትና ሐዘኗ ከልኩ አለፈ። ለአንዲት እናት ዓይንንና ልጅን በአንዴ ማጣት እጅግ ጭንቅ ነው። በሌሊት ግን ቅዱስ ለንጊኖስ በራእይ ተገልጦ ደስታ ነገራት።

"ልጅሽ በገነት ሐሴትን ያደርጋል። አንቺ ግን ራሴን ከተቀበረችበት አውጪ።" አላት። ወደ ጠቆማት ቦታ በመሪ ስትቆፍር ብርሃን ወጥቶ ዓይኗ በራላት። በታላቅ ሐሴትም ቅድስት ራሱን ወደ ሃገሯ ወስዳታለች።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ኪርያቆስ <3

ሊቅነትን ከገዳማዊ ሕይወት የደረበው ቅዱስ ኪርያቆስ የቆረንቶስ ሰው ሲሆን አበው "ጥዑመ ቃል - አንደበቱ የሚጣፍጥ" ይሉታል። ገና በልጅነቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያነብ ከአንደበቱ ማማር ከነገሩ መሥመር የተነሳ ከጳጳሱ እስከ ሕዝቡ ድረስ ተደመው ያደምጡት ነበር።

በወጣትነቱ ጣዕመ ዓለምን ንቆ ከቆረንቶስ ኢየሩሳሌም ገብቷል። ቀጥሎም ወደ ፍልስጥኤም ተጉዞ የታላቁ አባ ሮማኖስ ደቀ መዝሙር ሁኖ መንኩሷል። በገዳሙ ለበርካታ ዘመናት ሲኖርም እጅግ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል።

በ፫፻፹፩ ዓ.ም መቅዶንዮስ፣ አቡሊናርዮስና ሰባልዮስ በካዱ ጊዜም ለጉባኤው ወደ ቁስጥንጥንያ ከሔዱ ሊቃውንት አንዱ ይሔው ቅዱስ ኪርያቆስ ነው። ወደ ጉባኤው የሔዱትም ከታላቁ ሊቅና የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ መንፈሳዊ ጋር ነው።

ሁለቱ እጅግ ወዳጆች ነበሩና። በጉባኤውም መናፍቃንን ረትተው፣ ሃይማኖትን አጽንተው፣ ሥርዓትን ሠርተው ተመልሰዋል። ቅዱስ ኪርያቆስም በተረፈ ዘመኑ በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል።

አምላከ አበው የወዳጆቹን የቅድስና ምሥጢር ለእኛም ይግለጽልን። በረከታቸውንም አትረፍርፎ ይስጠን።

ኅዳር ፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ጻድቅ (ዘደብረ በንኮል)
፪.ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ጻድቅ (የሠራዊት አለቃ)
፫.ቅዱስ ኪርያቆስ ሊቅ
፬.ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ንጉሥ (ልደቱ)
፭.ቅዱሳን አትናቴዎስና እኅቱ ኢራኢ (ሰማዕታት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
፬.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭.አቡነ ዜና ማርቆስ
፮.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)

"በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው። የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው። የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል።"
(ምሳሌ ፲፥፮-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአባ ጴጥሮስ ሣልሳዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ጴጥሮስ ሣልስ <3

"ጳጳስ" ማለት "አባት - መሪ - እረኛ" ማለት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ሥልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ ሦስት ናቸው። እነሱም ዲቁና፣ ቅስና፣ ጵጵስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ ዘጠኝ ያህል ክፍሎች አላቸው። ከእነዚህም ከፍተኛው ሥልጣን ጵጵስና ነው።

ጵጵስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው። ሥልጣኑ በምድር "ሸክም"፣ "ዕዳ" ሲሆን በሰማይ ግን "ክብር" ነው። ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ጵጵስናን አይመኝም።

ቅዱስ ጳውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ጵጵስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ።" (፩ጢሞ. ፫፥፩) ማለቱን ይዞ "ሹሙኝ" ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው። ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል። የከፋው ግን የጳጳሱ ነው።

አንድ ጳጳስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም። ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና። ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው።" (ዮሐ. ፲)
ስለዚህም ክህነት (ጵጵስና) ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ከባድም ኃላፊነት ነው።

አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የጵጵስና መንበሮችን መሥርተው ትምህርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል። ከእነዚህ መንበረ ጵጵስናዎች አራቱ የበላይ ናቸው። እነዚህም የቅዱስ ጴጥሮሱ የሮም፣ የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ፣ የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ጳውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው።

እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ ፬፻፵፫ (፬፻፶፩) ዓ.ም ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል። ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው።

የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው፣ ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ጳጳሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች፤ ታከብራለች።

በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን። እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና። ከእነዚህም መካከል አንዱ አባ ጴጥሮስ ሣልሳዊ ነው።

ሣልሳዊ መባሉ ከእርሱ በፊት በዚህ ስም ተጠርተው በመንበረ ማርቆስ ላይ የተቀመጡ ሁለት ፓትርያርኮች ስለ ነበሩ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ቀዳማዊ "ተፍጻሜተ ሰማዕት" (የሰማዕታት ፍጻሜ) የተባለው ሲሆን አሥራ ሰባተኛ ሊቀ ጳጳሳት ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ ካልዕ ደግሞ በ፫፻፸ዎቹ አካባቢ ሃያ አንደኛ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ የተሾመና የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ደቀ መዝሙር የነበረ አባት ነው። ዛሬ የምናስበው አባ ጴጥሮስ ደግሞ በ፬፻፸ዎቹ አካባቢ ሊቀ ጵጵስናን በግብጽ ተሹሞ ያገለገለውን ነው።

ወቅቱ መለካውያን (የኬልቄዶን ጉባኤ አማኞች) የሰለጠኑበት በመሆኑ ሁኔታዎች ትንሽ አስቸጋሪ ነበሩ። አንደኛ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት የተከፈለችበት ጊዜ በመሆኑ ፈተናው ለእረኞች ቀላል እንዳይሆን አድርጐታል። ሌላውና ዋናው ፈተና ግን በዘመኑ የነበሩ ነገሥታት ለመለካውያን (ለመናፍቃን) ወግነው ምዕመናንን ማሳደዳቸው ነው።

አባ ጴጥሮስ ከተመረጠ በኋላ አስቀድሞ ያደረገው አጋዥ መፈለግ ነበር። እግዚአብሔር ሲረዳው የታላቂቱ ሃገር የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ የሆነው ቅዱስ አካክዮስን አገኘ። ከእርሱ ጋርም ደብዳቤ ይጻጻፉ ያዙ።

ደብዳቤ ሲባል ግን እንዲህ እኛ በዘመኑ እንደምንጽፈው ያለ አይደለም። ይልቁን አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትን የተሞሉ ጦማሮች ነበሩ እንጂ። ሁለቱ አበው በየሃገራቸው እየዞሩ እየሰበኩ አልደርሱበት ባሉበት ቦታ ደግሞ ክታቦችን እየጻፉ በአንድነት ስለ ቀናች ሃይማኖት ደከሙ።

በእግዚአብሔር ቸርነትም ተሳካላቸው። አባ ጴጥሮስ በዚህች ቀን ሲያርፍ መሰሉ "ካልእ አትናቴዎስ" ተክቶታል። ከፈጣሪውም እሴተ ኖሎትን (የእረኝነት ዋጋውን) ተቀብሏል።

አምላከ አበው ጳጳሳት መንጋውን በርኅራኄ የሚጠብቁ እረኞችን ያድለን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ሣልስ
፪.አባ ሱንቱዩ ሊቀ ጳጳሳት
፫.ቅድስት ሴቴንዋ ነቢይት
፬.ቅድስት አንስጣስያ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)
፪.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
፭.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
፮.ሊቁ አባ ሕርያቆስ
፯.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ

"ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም። ግድ ደርሶብኝ ነውና። ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ። ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና። ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል። እንግዲህ ደመወዜ ምንድን ነው? ወንጌልን እየሰበክሁ በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ብናገር ነው።"
(፩ቆሮ. ፱፥፲፭-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ <3

ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል። "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ።" ይላቸዋል።
(ሉቃ. ፩፥፮)

የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና የዘካርያስ ደግሞ መቶ ደርሶ ነበር።

ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ፣ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው።

ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች። በስድስተኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው።

የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ ሰኔ ፴ ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል።

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእስራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሄሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ሲወለድ ደግሞ የከፈተ ዮሐንስ የሚባል ሕፃን አለና እርሱንም ግደል።" አሉት።

እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል። አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለሦስት (አምስት) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ አምስት (ሰባት) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት።

ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው። እርሷም ስደት ላይ ነበረችና። ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው። ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው። ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ።" አላት። ባርካው አጽናንታውም ተለያዩ።

ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ። ለሃያ አምስት (ሃያ ሦስት) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም።
ይህችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም።

ከዚህ በኋላ ሠላሳ ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው። "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ።" አለው። ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና።
(ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩)

አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. ፩፥፸፮) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና።

ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ። ያዩት ሁሉ ፈሩት፤ አከበሩት። ቁመቱ ቀጥ ያለ፣ ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ፣ ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ፣ መልኩ የተሟላና ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና።

ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው። በዚህ አገልግሎት ለስድስት ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ "አጥምቀኝ" ብሎ ሲመጣ ደነገጠ፤ የሚገባበትም ጠፋው።

"እንቢ ጌታዬ! አንተ አጥምቀኝ።" አለው። ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው፤ አጠመቀው። በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል።

ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው። ንጉሡም ተቀይሞ ለሰባት ቀናት አሠረው። ንጉሡ ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሄሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው። እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት።

አበው "እምሔሶ ለሄሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሄሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር።" ይላሉ። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል።
(ማቴ. ፫፥፩ ፣ ማር. ፮፥፲፬ ፣ ሉቃ. ፫፥፩ ፣ ዮሐ. ፩፥፮)

ርጉም ሄሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች። ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት።

ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ሥልጣን ሰጥቶ አሰናበታት። በመላው ዓለም ለአሥራ አምስት ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዐርፋለች።

ይህች ዕለት ለቅዱሱ "አስተርዕዮተ ርዕሱ" ወይም ቅድስት ራሱ ከተሰወረችበት የተገለጠችበት ነው።

ጥቅምት ፴ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ)
፫.ቅድስት ማርያም (እናቱ)
፬.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፭.አባ አብርሃም ገዳማዊ
፮.ቅዱስ ይስሐቅ ንጉሥ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፪.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፫.አባ ሣሉሲ ክቡር ጻድቅ

"..... እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሏት አንዲት አገልጋይ ትሰማ ዘንድ ቀረበች። የጴጥሮስ ድምጽ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሳ ደጁን አልከፈተችም። ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች።"
(ሐዋ ፲፪፥፲፪-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ይከታተሉን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለአበው ቅዱሳን ሳሙኤል ዘወገግ፣ ጸቃውዐ ድንግል እና ድሜጥሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ሳሙኤል ዘወገግ <3

ሃገራችን ኢትዮጵያ ማኅደረ ቅዱሳን (ምዕራፈ ቅዱሳን) እንደ መሆኗ ፍሬ ክብር፣ ፍሬ ትሩፋት ያፈሩ ብዙ አባቶችና እናቶችን አፍርታለች። ብርሃን ሁነው ካበሩላት ቅዱሳን መካከል አንዱ ደግሞ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ ናቸው።

በእኛው ሃገር ብቻ ብዙ "ሳሙኤል" የሚባሉ ቅዱሳን በመኖራቸው ስንጠራቸው "ዘእንትን" እያልን ነው።
ለምሳሌም፦
ሳሙኤል ዘዋሊ
ሳሙኤል ዘወገግ (የዛሬው)
ሳሙኤል ዘጣሬጣ
ሳሙኤል ዘቆየጻ
ሳሙኤል ዘሃሌ ሉያና
ሳሙኤል ዘግሺን መጥቀስ እንችላለን። ሁሉም የመካከለኛው ዘመን ሐዋርያዊ አባቶች ናቸው።

ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ የተወለዱት በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው የብዙ ቅዱሳን ቤት የሆነችው ሽዋ ናት። መንደራቸውም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ብዙም አይርቅም።

የጻድቁ ወላጆች እንድርያስና አርሶንያ የሚባሉ ሲሆን ደጐች ነበሩ። ጻድቁ በተወለደ ጊዜ የቤታቸው ምሰሶ ለምልሞ ተገኝቷል። አቡነ ሳሙኤል ከልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው በጉብዝናቸው ወራት ይህችን ዓለም ንቀዋል።

የታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው በደብረ ሊባኖስ መንነዋል። ከአሥራ ሁለቱ ኅሩያን (ምርጦች) አርድእት አንዱ ነበሩና በክህነታቸው ደብረ ሊባኖስን ተግተው ያጥኑ ነበር። በዚያውም በንጹሕ ልቡና በጾምና ጸሎት ይተጉ ነበር።

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ በደጉ ጳጳስ በአቡነ ያዕቆብ ዘመን አሥራ ሁለቱ ንቡራነ እድ ተመረጡ። እነዚህ አባቶች በወንጌል አገልግሎት በተለይ ደቡብና ምሥራቁን የሃገራችን ክፍል ያበሩ ናቸው። ቅዱሳኑ ሲመረጡም ከአቡነ ፊልጶስ ቀጥለው በሁለተኛ ደረጃ የተመረጡ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ ናቸው።

ሃገረ ስብከታቸውም ሐረርና ሱማሌ ነበር። ጻድቁ በሃገረ ስብከታቸው ወርደው በሐረርና ሱማሌ አካባቢ ለዘመናት የወንጌልን ዘር ዘርተው እልፍ ፍሬን አፍርተዋል። አካባቢውንም መካነ ቅዱሳን አድርገውታል።

ቀጥለው ገዳማዊ ሕይወትን ያጸኑ ዘንድ በምሥራቁ የሃገራችን ክፍል በአፋር ሱባኤ ገቡ። ቦታውም ደብር ሐዘሎ ነበር። በቦታው ለመቶ ሃምሳ አምስት ቀናት ከቆሙ ሳያርፉ፣ ከዘረጉ ሳያጥፉ፣ እህል ውኃ ሳይቀምሱ ጸለዩ።

በሱባኤያቸው ፍጻሜ ግን ቅዱስ መልአክ መጥቶ "ሳሙኤል ወደዚያ ተራራ ሒድ። የስምህ መጠሪያ እርሱ ነውና። ይህ ግን የሌላ ሰው (የአባ አንበስ ዘሐዘሎ) ርስት ነው።" አላቸው። ጻድቁም ወዳላቸው ተራራ ሒደው ቢጸልዩ ከሰማይ ብርሃን ወረደላቸው።

በመንፈቀ ሌሊት የበራው ብርሃን እስከ ጐረቤት መንደር ሁሉ በመድረሱ የአካባቢው ሰው "ወገግ አለኮ - ነጋ" ብለዋል። በዚህ ምክንያት ዛሬም "ደብረ ወገግ" ይባላል። ይህ ቦታ ዛሬም ድረስ ንጹሕ ልብ ላላቸው አበው በብርሃን ተከቦ ይታያል።

ጻድቁ የወለዷቸው ብዙ ሥውራንም በሥፍራው ይገኛሉ። ቦታው የአንበሶች መኖሪያ በመሆኑ ጠላት መናንያኑን ማጥቃት አይችልም። ሳሙኤል ዘወገግም የሚጸልዩት በአናብስት ተከበው ነበር።

በቦታው አንዳንዴም አንበሶች ሲሰግዱ ይታያል። ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ግን እንዲህ በቅድስና ተመላልሰው በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሱማሌ ክልል ውስጥ በዚህች ቀን ዐርፈዋል። የጻድቁ ልደት ሐምሌ ፲ ሲሆን ፍልሠታቸው ደግሞ ግንቦት ፳፯ ነው።

<3 አባ ጸቃውዐ ድንግል <3

እኒህ ጻድቅም ኢትዮጵያዊ ናቸው:: የስማቸው ትርጉም "የድንግል ማርያም ወለላ ማር" ማለት ሲሆን ዜና ሕይወታቸው እንደ ስማቸው ጣፋጭ ነው።

የእኒህ ጻድቅ አባታቸው የተመሰከረላቸው ሊቅና የገዳም መምህር ናቸው። ምክንያቱም ጸቃውዐ ድንግልን ከወለዱ በኋላ መንነዋልና። አባት የደብረ ዘኸኝ መምህር ሳሉ ልጃቸው ጸቃውዐ ድንግልን ወደ ገዳሙ ወስደው አሳደጓቸው።

በዚያውም ጾምና ጸሎትን፣ ትዕግስትና ትሕርምትን አስተማሯቸው። ቅዱሳት መጻሕፍትንም በወጉ አስጠኗቸው። አባ ጸቃውዐ ድንግልም በጐውን የምናኔ ጐዳና ከተማሩ በኋላ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበሉ።

አርባ ዓመት ሲሞላቸው ግን አባታቸው ዐረፉ። መነኮሳት አበውም ተሰብስበው "ከአንተ የተሻለ የለም።" ሲሉ ጸቃውዐ ድንግልን የደብረ ዘኸኝ መምህር አድርገው ሾሟቸው። ጻድቁም ቀን ቀን ሲያስተምሩ ይውሉና ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ ያድሩ ነበር።

በሌሊትም ከባሕሩ ወጥተው የአካላቸው ርጥበት ደርቆ ላበታቸው እስኪንጠፈጠፍ ድረስ ይሰግዱ ነበር። በዚህ መንገድም ራሳቸውን ገዝተው፣ መነኮሳትንም ገርተው ያዙ። እግዚአብሔርም ክብራቸውን ይገልጽ ዘንድ ብዙ ተአምራትን በእጃቸው አሳይቷል።

አንድ ቀን አባ ጸቃውዐ ድንግል መንገድ ሲሔዱ ሁለመናው በቁስል የተመታ አንድ መጻጉዕ ነዳይ ወድቆ አዩ። ወደ እርሱ ሲደርሱ ምጽዋትን ለመናቸው። ጻድቁ ግን "የምሰጥህ ነገር የለኝም። ግን የፈጣሪዬን ስጦታ እሰጥሃለሁ።" ብለው በውኃ ላይ ጸልየው ረጩት።

ያ መጻጉዕም አካሉ ታድሶ እንደ እንቦሳ ዘሎ ተነሣ። ደስ እያለው ፈጣሪውንም እያከበረ ወደ ቤቱ ሒዷል። አባ ጸቃውዐ ድንግልም በዚህች ቀን ዐርፈው በገዳማቸው ተቀብረዋል።

<3 ቅዱስ ድሜጥሮስ ሰማዕት <3

ይህ ቅዱስ በዘመነ ሰማዕታት በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከነበሩ ክርስቲያኖች አንዱ ነው። ቅዱስ ድሜጥሮስ ስቅጣር ከሚባል ደግ ባልንጀራው ጋር በበጐው ጐዳና ሲኖሩ የመከራው ዘመን ደረሰ። መወሰን ነበረባቸውና ፈጣሪያቸውን ከሚክዱ ሞትን መረጡ።

አስቀድሞም ሲያስተምር በመገኘቱ ቅዱስ ድሜጥሮስ በንጉሡ እጅ ወደቀ። ንጉሡ መክስምያኖስም እሥራትን አዘዘበት። በዚያ ወራት ደግሞ የንጉሡ ወታደር የሆነና በጣዖት የሚመካ አንድ ጉልበተኛ ነበር።

ማንም በትግል አሸንፎት ስለማያውቅ ጣዖታዊው ንጉሥ ይመካበት ነበር። አንድ ቀን ግን አንድ ክርስቲያን ወደ እሥር ቤት ገብቶ ቅዱስ ድሜጥሮስን "ባርከኝና ያንን ጣዖታዊ ጉልበተኛ እጥለዋለሁ።" አለው።

የቅዱሱን ጸሎትና በረከት ተቀብሎም በንጉሡ አደባባይ ታግሎ ጣለው። ንጉሡና የጣዖቱ ካህናትም በእጅጉ አፈሩ። በኋላ ግን ይህንን ያደረገው ቅዱስ ድሜጥሮስ መሆኑ በመታወቁ ከባልንጀራው ቅዱስ ስቅጣር ጋር በዚህች ቀን ገድለዋቸዋል።

አምላከ አበው ቅዱሳን ጸጋ ክብራቸውን ያብዛልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ጥቅምት ፳፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ሳሙኤል ጻድቅ (ዘደብረ ወገግ)
፪.አባ ጸቃውዐ ድንግል (ዘደብረ ዘኸኝ)
፫.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ስቅጣር ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.የፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
፪.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፬.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊት
፭.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ
፮.ቅድስት አርሴማ ድንግል

"በእሽቅድምድም ሥፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል። እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው። እኛ ግን የማይጠፋውን።"
(፩ቆሮ ፱፥፳፬-፳፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"መድኃኔ ዓለም ሆይ! ስለ ኃጢአቴ ሥርየት በጭንቅና በመከራ ምስጋናህን ዘወትር አቀርባለሁ።
ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ! የሰማይና የምድር ጌታ እንደ መሆንህ እኔ ጎስቋላው አገልጋይህ ኃጢአቴን ይቅር ብለህ ማደሪያዬን ስጠኝ እያልኩ በምለምንህ ጊዜ በዱርም ቢሆን በተራራ ላይ በአስፈላጊው ቦታ ሁሉ በፍላጎቴ መጠን ምግቤን አዘጋጅልኝ።"
(መልክአ መድኃኔ ዓለም)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለፈጣሪያችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እና ለቅዱሳኑ አባ መቃርስ፣ አቡነ መብዓ ጽዮን ወአባ ጽጌ ድንግል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ <3

ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት።
ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አስረው ሲደበድቡት አድረዋል።
ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት።
ምራቃቸውን ተፉበት፤ ዘበቱበት።
ራሱንም በዘንግ መቱት።
እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ።

በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት። በሠለስት (ሦስት ሰዓት ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ገረፉት።
ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። ስድስት ሰዓት ላይ በረዣዥም ብረቶች አምስት ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት። ሰባት ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ።

ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ ሰባት ቃላትን ተናገረ። ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በባሕርይ ሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ።
በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ። አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት።
በዚያች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ። ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ልቅሶን አለቀሰ። ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ።

ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለው መጋቢት ፳፯ ቀን ቢሆንም በዓሉ ወደ ጥቅምት እንዲመጣ ያደረጉት አበው ሊቃውንት ናቸው። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ መጋቢት ፳፯ የሚውለው ዐቢይ ጾም ውስጥ በመሆኑና የንግሥ በዓላት በዐቢይ ጾም ስለማይፈቀዱ ነው።

ምንም እንኳ በቅርብ ጊዜ በዐቢይ ጾም የሚያነግሡ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም አባቶቻችን ግን እንዲህ ያለውን ሥርዓት አላቆዩልንም። ከበሮና የቸብቸቦ ዝማሬም በወቅቱ የተፈቀደ አይደለም። በዚህም ምክንያት የበዓለ ስቅለት ንግሡ ወደ ጥቅምት ፳፯ ሲመጣ፣ የመጋቢት ፭ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ንግሥ ወደ ጥቅምት ፭፣ የመጋቢት ፲ መስቀል ወደ መስከረም ፲፯ መጥቶ እንዲከበር ሆኗል።

<3 ቅዱስ መቃርስ ብፁዓዊ <3

በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን ብዙ ናቸው። "ታላቁ መቃርዮስ"፣ "መቃርስ እስክንድርያዊ"፣ "መቃርስ ባሕታዊ"ን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ይህኛው ቅዱስ ደግሞ "መቃርስ ኤጲስ ቆጶስ፣ መቃርስ ብፁዓዊ፣ መቃርስ ዘሃገረ ቃው" ይባላል። ሁሉም መጠሪያዎቹ ናቸው።

ቅዱሱ የአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰው ሲሆን የቅዱስ ቄርሎስና የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ተከታይ ነው። ከሕይወቱ ማማርና ከቅድስናው መሥመር የተነሳ አበው አመስግነውት አይጠግቡም። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል።" እንዳለው።
(መዝ. ፺፩)

ዳግመኛ "ወይከውን ከመ ዕጽ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ" (መዝ. ፩፥፫) እንዳለው ቅዱስ መቃርስ እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን አፍርቷል። ከሁሉ አስቀድሞ በበርሃ ኗሪ ከሆነበት ቀን ጀምሮ ስለ ጌታ ፍቅር እንባው እንደ ዥረት እየፈሰሰ ራሱን በብረት ዘንግ ይመታ ነበር።

"ቃው" በምትባል ሃገር ጳጳስ ሆኖ በተሾመ ጊዜም ተጋድሎውን አልቀነሰም። ጳጳስ ቢሆንም የሚለብሰው የበርሃዋን ደበሎ ነው። ከብቅዓቱ የተነሳ የሕዝቡ ኃጢአት በግንባራቸው ላይ ተጽፎ እየታየው ስለ ወገኖቹ ያለቅስ ነበረ። በቤተ መቅደስ ውስጥ ቆሞ አንጀቱ ቅጥል እስኪል ድረስም ያለቅስ ነበር።

ሁልጊዜ ሲቀድስ ጌታችንን ከመላእክቱ ጋር ያየው ነበር። አንድ ቀንም ጌታ ቅዱስ መቃርስን "ጳጳሱ ሆይ ሕዝቡን ገስጻቸው። ብትገስጻቸውና ባይሰሙህ እዳው በእነርሱ ላይ ነው።" አለው። ቅዱስ መቃርስም ሕዝቡ ከኃጢአታቸው ይመለሱ ዘንድ ይመክራቸው፣ ይለምንላቸውም ነበር።

ከዚህ ሁሉ በኋላ በጉባኤ ኬልቄዶን (ጉባኤ አብዳን) ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ጳጳሳት ንጉሡን ፈርተው ሃይማኖታቸውን ሲክዱ ቅዱሳኑ ዲዮስቆሮስና መቃርስ "ተዋሕዶን አንክድም።" በማለታቸው ዘበቱባቸው። ብዙ አሰቃይተውም ወደ ጋግራ ደሴት አሳደዷቸው።

ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጋግራ ውስጥ ሲሞት ቅዱስ መቃርስ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ሕዝቡን ሲመክር ያዙት። ከመሬት ላይ ጥለውም እየደጋገሙ ኩላሊቱን ረገጡት። ከመከራው ብዛትም በዚህች ቀን ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። ቅዱሱ ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል።

አበውም ስለ ቅዱስ መቃርስ ብሎ ጌታ እንዲምራቸው እንዲህ ይጸልዩ ነበር፦
"ሰላም ሰላም ለፈያታዊ ዘቀደሶ።
ሃገረ ጽጌ የአኀዝ ምስለ ጻድቃን በተዋርሶ።
ተዘከረኒ ክርስቶስ አመ ትመጽእ ለተዋቅሶ።
በእንተ መቃርስ ጻድቅ እንተ መጠወ ነፍሶ።
ወበበትረ መስቀል ዘይዘብጥ ርዕሶ።"
(አርኬ ዘጥቅምት ፳፯)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት <3

ከሁሉ አስቀድሞ ስለ ሰማዕታት ዜና ሲሰማ ለዚህ ቅዱስ አንክሮ (አድናቆት)፣ ክብርና የጸጋ ውዳሴ ይገባዋል። ምክንያቱም ገድለ ሰማዕታትን የጻፈልን እርሱ ነውና። ነገር ግን መጻፍ ሲባል ነገሮች እንዲህ እንደ እኛው ዘመን ቀላል እንዳይመስሏችሁ። ቅዱሱ ዜና ሰማዕታትን ለማዘጋጀት ሃብቱን፣ ንብረቱን፣ ቤተሰቦቹንና ሕይወቱንም ሰውቷል።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በመጨረሻው ዘመነ ሰማዕታት (በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ዓለም በደመ ሰማዕታት ስትሞላ እንኳን የሰማዕታቱን ዜና የሚጽፍ ሥጋቸውን እንኳ የሚቀብር አልተገኘም። "ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ - የሚቀብራቸውም አጡ።" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት።
(መዝ. ፸፰፥፫)

እግዚአብሔር ግን ስለ ወዳጆቹ ሰማዕታት ይህንን ቅዱስ አስነሳ። ቅዱስ ዮልዮስ በዘመኑ ደግ ክርስቲያን፣ ትዳርና ልጆች ያሉት፣ እጅግ ባለ ጸጋና ሦስት መቶ አገልጋዮች ያሉት ምጽዋትን የሚወድ ሰው ነበር።

በወቅቱ የክርስቲያኖች በየመንገዱ ወድቀው መታየታቸው ዕረፍት ቢነሳው ከቤተሰቦቹ ጋር መክሮ መልካም ግን ደግሞ ከባድ ውሳኔን አስተላለፈ። ውሳኔውንም ታጥቆ ይተገብረው ጀመር። በእውነት ድንቅ ሰው ነው። በምን እንመስለዋለን! እርሱን የፈጠረውን ጌታ "ዕጹብ ዕጹብ" ብለን ከማድነቅ በቀር።

ሰማዕታቱም ስለ ደግነቱ የሚመልሱለት ቢያጡ ዝም ብለው ይመርቁት ነበር። እንዲህ እንዲህ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ሊፈጸም ወራት ቀሩት። በዚህ ጊዜ ለሰማዕትነት ከመነሳሳቱ የተነሳ ጌታችንን ተማጸነ። ጌታችንም ተገልጾለት "ሒድና ሰማዕት ሁን፤ ፈቅጄልሃለሁ።" አለው። እርሱም ደስ እያለው ዜና ሰማዕታቱን ለሁነኛ ሰው ሰጥቶ ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፈለ።

ቀጥሎም ቤተሰቦቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ ወደ ሃገረ ገምኑዲ ሔደ። በመኮንኑ ፊት የክርስቶስን አምላክነት ቢመሰክር ፈጽመው አሰቃዩት። በማግስቱም ወታደሮቹ ለጣዖት ካልሰገድክ ሲሉት "ቆዩማ ላሳያችሁ።" ብሎ በጸሎቱ ጣዖታትን ከነ ካህናቶቻቸው ምድር ተከፍታ እንድትውጣቸው አደረገ። በተአምሩም መኮንኑና ሠራዊቱ አምነው ተከተሉት።

በፍጻሜውም የሌላ ሃገር መኮንን ቅዱስ ዮልዮስን ከቤተሰቡና ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ያህል ተከታዮቹ ጋር ሁለቱን የሃገር ገዥዎች ጨምሮ አንገታቸውን አሰይፏቸዋል።

አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን። በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን።

ጥቅምት ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፪.አባ ዕብሎይ ገዳማዊ
፫.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
፬.ቅዱሳን አብርሃምና ሐሪክ
፭.ቅዱሳን አሞኒና ሙስያ (የታላቁ ዕብሎይ ወላጆች)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.ቅዱስ አቡፋና ጻድቅ
፮.ታላቁ አባ ቢጻርዮን

"እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ።
መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል። ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።"
(ማቴ ፲፮፥፳፬-፳፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ገዳማዊ ቅዱስ አብላርዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ <3

በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ (ዓቢይ) THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው። አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን።

ታላቁ ቅዱስ አብላርዮስ ደግሞ ካለ ማመን ወደ ማመን፣ ከማመን ወደ መመንኮስ፣ ከመመንኮስ ወደ መጋደል፣ ከመጋደል ወደ ትሕርምት፣ ከዚያም ወደ ፍጹምነት የደረሰ በምድረ ሶርያም ገዳማዊ ሕይወትን ያስፋፋ አባት ነው።

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው። በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል። ሕይወቱ በጐላ በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው።
ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ፣ እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል።

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለአርባ ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል፤ አስተምሯል። በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት።

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። አኗኗራቸውም በቡድንም፣ በነጠላም ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው። ይሕም ሲያያዝ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደረሰ። በዚህ ዘመን ግን አባ ጳውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው። ለሰማንያ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ። ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ።

ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት። በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ። ስለዚህም አባ እንጦንስ "የመነኮሳት አባት" ተባሉ።

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል። ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል። ከእነዚህም አንዱና ዋነኛው ዛሬ የምናከብረው ታላቁ ጻድቅ አባ አብላርዮስ ነው።

ቅዱስ አብላርዮስ ሶርያዊ ሲሆን የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው። በቀደመ ሕይወቱ ክርስትናን ፈጽሞ የማያውቅ ሰው ነበር። ለዚህ ምክንያቱ የወላጆቹ ኢ-አማንያን መሆን ነው።

ገና በልጅነቱ ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ የግሪክን ፍልስፍና፣ የዮናናውያንን ጥበብ ተምሮ ፈላስፋ ሁኗል። በአሥራ ስድስት ዓመቱም በምድረ ሶርያ አሉ ከሚባሉ የጥበብ ሰዎች አንዱ ሆነ። ቅዱሱ ማንበብና መጠየቅን አብዝቶ ይወድ ነበር።
የሚያነበው ነገር በሶርያ ቢያጣ በአሥራ ሰባት ዓመቱ ተጨማሪ ጥበብን (እውቀትን) ፍለጋ ወደ ግብጽ (እስክንድርያ) ወረደ። በዚያ ግን ከሰማቸው ትምህርቶች አንዱ ልቡን ገዛው። በወቅቱ በግብጽ ላይ ፓትርያርክ የነበረው ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ስለ ምድራዊው ያይደለ ስለ ሰማያዊው ጥበብ ሲያስተምር ሰምቶ ተገረመ።

ቅዱስ አብላርዮስ በዚህ ሰዓት የሰበሰባቸውን የፍልስፍና መጻሕፍት ጥሎ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነብ ጀመረ። ቅዱስ እለ እስክንድሮስም የሚከብድበትን እያፍታታ ተረጐመለት። በአጭር ጊዜም ክርስቲያን ሆኖ ተጠመቀ።

በዚያው ዓመትም ከከተማ ወጥቶ ወደ በርሃ ገባ። ከአባ እንጦንስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሆኖ መነኮሰ። በዚያም በጾምና በጸሎት፣ በመታዘዝና በትሕትና ለዓመታት ኖረ። ቀጥሎም ወሬ ነጋሪ መጥቶ ወላጆቹ ማረፋቸውን ነገረው። በዚህ ጊዜ ቅዱስ አብላርዮስ ከአባ እንጦንስ ዘንድ ተባርኮ ማኅበሩን ተሰናብቶ ሶርያ ገባ። የወላጆቹን ሃብትና ንብረት በሙሉ መጽውቶ ወደ ሶርያ በርሃ ወጣ። በወቅቱ በአካባቢው ምንኩስና እየተነቃቃ ነበርና የቅዱሱ መምጣት ይበልጥ አጠናከረው።

ታላቁን ሊቅ ቅዱስ ኤጲፋንዮስን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትንም አፈራ። በአካባቢውም ታላቅ መካሪ፣ ናዛዥ፣ አጽናኝና መሪ ሆነ። ከብዙ ተአምራቱ ባለፈ ሃብተ ትንቢት የተሰጠው አባት ነውና እጅግ ክቡር ነበር።
የገድሉን ነገርማ ማን ተናግሮ ይፈጽመዋል!
እርሱ ከዕለተ ሰንበት በቀር እህልን አይቀምስም። ለዚያውም እሑድ በነግህ (ጧት) ትንሽ ሳር ነጭቶ ከመብላት በቀር ሌላ የሚበላው አልነበረውም። እንዲህ ባለ የበርሃ ሕይወት ለስልሳ ሦስት ዓመታት ኖረ። በዓለም የኖረበትን አሥራ ሰባት ዓመት ብንደምረው ሰማንያ ይሆናል። ቅዱሱ በተወለደ በሰማንያ ዓመቱ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዚህች ቀን ዐርፏል።

አምላከ ቅዱስ አብላርዮስ ጥበቡን፣ ፈሊጡን፣ ሕይወቱን ይግለጽልን። ከበረከቱም አይለየን።

ጥቅምት ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ
፪.ቅድስት ጸበለ ማርያም
፫.ቅድስት አውስያ
፬.አባ ጳውሎስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምህረ ትሩፋት)
፪.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፫.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
፬.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤጲስቆጶስ)
፭.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮.ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል)
፯.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮጵያዊ)
፰.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

"ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁን ተመልከቱ። እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣ ኃይለኞች የሆኑ ብዙዎች፣ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝነት መረጠ።
.....ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። ነገር ግን የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ።"
(፩ቆሮ ፩፥፳፮-፴)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ <3

በእስክንድርያ (ግብጽ) ሊቀ ጵጵስናን ከተሾሙና በጐ ሥራን ከሠሩ አበው አንዱ አባ ዮሴፍ ነው። እርሱ ለግብጽ ሃምሳ ሁለተኛ ፓትርያርክ ነውና በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ እንደ ነበር ይታመናል።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በግብጽ የሚኖሩ የዘመኑ ክርስቲያን ባልና ሚስት ወደ ፈጣሪ ለምነው ልጅ ሲወልዱ 'ዮሴፍ' አሉት። እጅግ ሃብታሞች ቢሆኑም እርሱ ገና ልጅ እያለ ሁለቱም ዐረፉ። ሕፃኑ ዮሴፍም ዕጓለ ሙታን (ወላጅ አልባ) ሆነ። ሕፃኑ ሲያለቅስ የተመለከተ አንድ ደግ ጐረቤቱ ግን ወደ ቤቱ ወሰደው።

እንደ ልጁ ተንከባክቦ ክርስትናንም አስተምሮ አሳደገው። እድሜው ሃያ ሲደርስም "የወላጆችህን ንብረት ንሳ።" ብሎ አወረሰው። ወጣቱ ዮሴፍ ግን "አኮኑ ዝንቱ ኩሉ ኃላፊ - ይህ ሁሉ ሃብት ጠፊ አይደለምን?" ብሎ ናቀው።

ለነዳያንም በትኖት እያመሰገነ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገሰገሰ። በዚያም የአሞክሮ ጊዜውን ፈጽሞ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበለ። ለዓመታትም በዲቁና ገዳሙን እያገለገለ፣ እየተጋደለ ኖረ።

የአባ ዮሴፍን ደግነት የሰማው የወቅቱ ፓትርያርክ አባ ማርቆስም ከገዳም አውጥቶ በመንበረ ጵጵስናው እንዲራዳውና ሕዝቡን እንዲያስተምርለት ወደ ከተማ አመጣው።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን አባ ዮሴፍ ወደ ፓትርያርኩ አባ ማርቆስ ቀርቦ "አባቴ! ወደ ገዳሜ አሰናብተኝ። ለመነኮስ በከተማ መኖር ፍትሕ አይደለምና።" ሲል ተማጸነው። ፓትርያርኩም "እሺ" ብሎ ቅስናን ሹሞ አሰናበተው።

ወደ ገዳመ አስቄጥስ ከተመለሰ ጀምሮ አባ ዮሴፍ በዓት ለየ። እስከ ሃምሳ ዘጠኝ ዓመቱም ድረስ በጾምና በጸሎት በበዓቱ ጸንቶ ኖረ። በአጠቃላይ በገዳም የኖረባቸው ዓመታትም ሠላሳ ዘጠኝ ደረሱ።

በዚህ ጊዜ ግን የወቅቱ ፓትርያርክ አባ ስምዖን (ከአባ ማርቆስ በኋላ ሦስት ፓትርያርኮች ዐርፈዋል።) በማረፉ ግብጽ እረኛን ስትፈልግ ነበር። 'ማንን እንሹም?' እያሉ ሲጨነቁ አንድ ሰው ጉቦ ሰጥቶ ሊሾም መሆኑን አበው ሰሙ። ይህ ሰው ደግሞ ጭራሹኑ ልጅ ያለው ነው።

አባቶች ተሯሩጠው ያ ጉቦኛ ባለ ሚስት እንዳይሾም አደረጉ። ቀጥለው ማንን እንደ ሚሾሙ ሲጨነቁ የሁሉም ሕሊና ስለ አንድ ሰው (አባ ዮሴፍ) ያስብ ነበር። ሁሉም ተሰብሳቢዎች ስለ ነገሩ ተጨዋውተው አባ ዮሴፍን ይሾሙ ዘንድ ቆረጡ።

ተሰብስበው በመንገድ ላይ ሳሉም እንዲህ ተባባሉ። "ወደ በዓቱ ስንደርስ ቤቱ ክፍት ከቆየን ፈቃደ እግዚአብሔር ነው። ዝግ ከሆነ ግን ፈጣሪ አልፈቀደም ማለት ነው።" ሲሉ ተስማሙ። ምክንያቱም የአበው በዓት ቶሎ ቶሎ አይከፈትምና።

ነገሩ ጥበበ እግዚአብሔር ነበረበትና ልክ ሲደርሱ እንግዳ ሊሸኝ በዓቱን ከፍቶ አገኙት። እንዳያመልጣቸው ተረባርበው ያዙት። ግጥም አድርገው አሥረው "አክዮስ - ይደልዎ - ይገባዋል።" እያሉ ሥርዓተ ሲመት አደረሱለት። እርሱ (አባ ዮሴፍ) ግን "እኔ ኃጢአተኛ ነኝ። አይገባኝም፣ ልቀቁኝ።" እያለ ይጮህ ነበረ።

አበው ግን ሥርዓተ ሲመቱን ፈጽመው ወስደው በመንበረ ጵጵስና በቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። በቁጥርም ሃምሳ ሁለተኛ ሁኖ ተቆጠረ። አምላክ ደጉን ሰው ጠቁሟቸዋልና ለቤተ ክርስቲያን ይተጋ ጀመር።

ሕዝቡን እያስተማረ፣ አብያተ ክርስቲያናትን እያነጸ፣ መጻሕፍትን እየተረጐመ፣ ተአምራትን እየሠራ፣ በመንኖ ጥሪት ለአሥራ ዘጠኝ ዓመታት አገልግሏል። ወቅቱም ተንባላት (አማሌቃውያን) በምድረ ግብጽ የሰለጠኑበት ነበርና ብዙ ችግሮችን አሳልፏል።

የግብጹ ሱልጣንም ሊገድለው ሁለት ጊዜ ሞክሮ አልተሳካለትም። ሁለት ጊዜም ለአባ ዮሴፍ የሰነዘረው ሰይፍ በመልአክ እየተመለሰ ተመልክቶ ትቶታል። አባ ዮሴፍ በዘመኑ ተሰዶ የነበረውን የኢትዮጵያ ጳጳስ አባ ዮሐንስንም ከተሰደደበት ወደ ሃገራችን እንደ መለሰው በዜና ሕይወቱ ተጽፏል። አባ ዮሴፍ እንዲህ ተመላልሶ በሰባ ስምንት ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፏል።

ቸር አምላክ በጻድቁ ሊቀ ጳጳሳት ጸሎት ይማረን። ከበረከቱም ይክፈለን።

ጥቅምት ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ዮሴፍ ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
፪.ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ኢላርዮስ
፬.ቅድስት እለእስክንድርያ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እስራኤል)
፬.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮.አባ ሳሙኤል
፯.አባ ስምዖን
፰.አባ ገብርኤል

"ኤጲስ ቆጶስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና። የማይኮራ፣ የማይቆጣ፣ የማይሰክር፣ የማይጨቃጨቅ፣ ነውረኛ ረብ የማይወድ፣ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፣ በጐ የሆነውን ነገር የሚወድ፣ ጠንቃቃ፣ ጻድቅ፣ ቅዱስ፣ ራሱን የሚገዛ ይሁን።"
(ቲቶ ፩፥፯-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ያግኙን።

Читать полностью…
Subscribe to a channel