gedlekidusan | Unsorted

Telegram-канал gedlekidusan - ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

3467

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Subscribe to a channel

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን ኢየሱስ ሞዐ ወአቡነ ሃብተ ማርያም እና ለናግራን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ <3

እግዚአብሔር በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ባያስነሳ ኑሮ ምናልባትም ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በምናያት መንገድ ላናገኛት እንችል ነበር። እውነተኛ አባቶቻችን ፈጽሞ ከሚቆረቁራቸው ነገር አንዱ የጻድቅና ሐዋርያዊ አባት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መዘንጋት ነው።

እርሳቸው ፍሬ ሃይማኖት ሆነው ከጽድቅ ፍሬአቸው አዕላፍ ቅዱሳንን ወልደው ሃገራችን በወንጌል ትምህርትና በገዳማዊ ሕይወት እንድታሸበርቅ አድርገዋል። እስኪ በዕለተ ዕረፍታቸው ስለ ጻድቁ ጥቂት ነገሮችን እናንሳ።

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ የተወለዱት ጐንደር የድሮው ስማዳ (ዳኅና) አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ዘክርስቶስና እግዚእ ክብራ ይባላሉ። የተወለዱት በ፲፪፻፲ ዓ/ም ነው። ነገር ግን አንዳንድ ምንጮች በ፲፩፻፺፮ ዓ/ም ያደርጉታል።

ጻድቁ ከክርስቲያን ወላጆቻቸው ጋር እንደሚገባ አድገዋል። በልጅነታቸው በብዛት ወላጆቻቸውን ያግዙ ነበር። በትርፍ ጊዜአቸው ደግሞ ትምሕርተ ሃይማኖትንና ሥርዓቱን ያጠኑ ነበር። በ፲፪፻፵ ዓ/ም ግን (ማለትም ሠላሳ ዓመት ሲሞላቸው) ይህቺን ዓለም ይተዋት ዘንድ አሰቡ።

አስበውም አልቀሩ ፈጣሪን እየለመኑ ደብረ ዳሕሞ ገቡ። በወቅቱ ዳሞ የትምህርትና የምናኔ ማዕከል ከመሆኑ ባሻገር የአቡነ አረጋዊ አምስተኛ የቆብ ልጅ ካልዕ ዮሐኒ ነበሩና የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ሆኑ።

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ በደብረ ዳሞ በነበራቸው ቆይታ ቀን ቀን ሲታዘዙ፣ ሲፈጩ፣ ውኃ ሲቀዱ ውለው ሌሊት እኩሉን በጸሎት በስግደትና የቀረውን ሰዓት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ አሳለፉ።

በመጨረሻም ልብሰ ምንኩስናን ለበሱ። ይህን ጊዜ ሠላሳ ሰባት ዓመታቸው ሲሆን ዘመኑም ፲፪፻፵፯ ዓ/ም ነው። ወዲያውም በዳሞ ሳሉ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ "ወደ ወሎ ሐይቅ ሒድ፤ ብዙ የምትሠራው አለና።" አላቸው።

በአንዴም ከዳሞ (ትግራይ) ነጥቆ ሐይቅ እስጢፋኖስ (ወሎ) አደረሳቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ መቅደስ በተጋድሎ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በማዕጠንትና ሐይቁ ውስጥ ሰጥሞ በመጸለይ ኖሩ።

ቅድስናቸውን የተመለከቱ አበውም በግድ አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው። ይህ ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቁ መሠረት የተጣለበት አጋጣሚ።
ነገሩ እንዲህ ነው፦
ስም አጠራሯ የከፋ ዮዲት ጉዲት ለአርባ ዓመታት ሃገሪቱን እንዳልነበረች ብታደርጋት ክርስትና ተዳከመ፤ ባዕድ አምልኮም ነገሠ። አቡነ ኢየሱስ ሞዐ (ትርጉሙ ኢየሱስ ክርስቶስ አሸነፈ ማለት ነው።) ደግሞ ሃይማኖታቸው የቀና ከስምንት መቶ በላይ ክርስቲያኖችን ሰበሰቡ።

በሃገሪቱ ትልቅና የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ቤተ መጻሕፍት አደራጁ። እነዚያን አርድእት በቅድስናና በትምህርት አብስለው አመነኮሱና "ሒዱ! ሃገሪቱን ታበሩ ዘንድ ተጋደሉ።" ብለው አሰናበቷቸው።

ከእነዚህ መካከልም ታላላቁን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን፣ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እና የኋላውን ፍሬ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን መጥቀስ እንችላለን። በዚህም ምክንያት ጻድቁ "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን - አእላፍ ቅዱሳንን የወለደ" ሲባሉ ይኖራሉ።

ጻድቁ ከዚህ በተጨማሪ የወቅቱን ንጉሥ አፄ ይኩኖ አምላክን በማስተማር ለሃገርና ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ሰው አድርገዋል። በግላቸው ሐይቅ ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ የብርሃን ምሰሶ ይወርድላቸው ነበር። ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም ከጠፋ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ አቅንተዋል።

እንዲህ ለቤተ ክርስቲያን ሲተጉ በተለይ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው አርባ አምስት ዓመታት ለዓይናቸው እንቅልፍን አላስመኙትም። ጐድናቸውም ከመኝታ ጋር ተገናኝቶ አያውቅም።
"እንዘ የኀሊ ዘበሰማያት ዐስቦ
መጠነ ዓመታት ሃምሳ ኢሰከበ በገቦ።" እንዲል።

ከዚህ በኋላ የሚያርፉበት ዕለት ቢደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። በተወለዱ በሰማንያ ሁለት ዓመታቸው (በሰማንያ ስድስት ዓመታቸው የሚልም አለ።) በ፲፪፻፹፪ ዓ/ም በዕለተ ሰንበት ዐርፈው ተቀብረዋል።
ጻድቁ ስም አጠራራቸው እጅግ የከበረ ነው!

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር) ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ መርቆሬዎስ ኃያል <3

ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት። ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው።

ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት "ካልዕ (ሁለተኛው) ሊቀ ሰማዕታት" ሲሉ ይገልጹታል።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር "አሮስ" የሚሉት ሰው ይኖር ነበር። ሚስቱ ደም ግባት የሠመረላት እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር።

አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ። እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ። የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል "እንስሳ ተያዘልን።" ብለው ሲሯሯጡ ዓይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው። ሁለት ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ውስጥ ተይዘው ነበር።

እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው። ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል። ግን እጅግ ግዙፍ፣ ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ፣ ወገባቸው እንደ ሰው፣ ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት የሚመስል ነው።

እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም። አንበሳና ነብርን እንኳ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል። ዓይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም። ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ። ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት። አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው።

"ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት።" አላቸው። ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው። በዚህ ጊዜ ሁለቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት። አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶ ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት።

ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች። ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት። ትርጉሙም "መፍቀሬ አብ - የአብ ወዳጅ" ማለት ነው። ከዚያም አሮስ ሚስቱን፣ ልጁንና ሁለቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ ተጠመቀ።

አበው ካህናት እሱን "ኖኅ"፣ ሚስቱን "ታቦት"፣ ልጁን ደግሞ "መርቆሬዎስ" ሲሉ ሰየሟቸው። መርቆሬዎስ ማለትም "ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ - የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው።

ከዚያም ደስ እያላቸው፣ ክርስቶስን እያመለኩ፣ ነዳያንን እያሰቡ፣ ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ። ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ "ካላመጣሃቸው" አለው። ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ።

ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው። በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር። አንድ ጊዜ ግን ሁለቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው። ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል "እንቢ" በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ።

በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ። ንጉሡ ደግሞ ታቦትን "ላግባሽ" ስላላት የአምስት ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች። በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው።

እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር። በኋላ ግን በሕፃኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው። በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው። በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ።

በዚያም ቤተ ክርስቲያንን አንጾ፣ ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጐ ኖኅ ለዓመታት ኖረ። ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ። እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት።

በጦርነት እጅግ ኃያል በሰው ዘንድ ፍጹም ተወዳጅ የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ። ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምዕመናን ላይ ሞት ታወጀ። በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግሥት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸው ዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ።

ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ። ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው።

በማግስቱም "ምን ይሻላል?" ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ "እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻየን እቋቋማቸዋለሁ።" ቢል ሳቁበት።

እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው።) ተጭኖ በርበሮችን "ጠብ ይቅርባችሁ፤ በሰላም ሒዱ።" ቢላቸው ተሳለቁበት። ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ። ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኳ የተረፈ አልነበረም።

ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ። ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ "ድሉ የጣዖቶቼ የነ አጵሎን ነው።" በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ።

በሦስተኛው ቀንም "ለጣዖት ሠዋ" የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ። ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ። የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው።

"ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ - ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ ለጥፋት ይሁንህ።" ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው። ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው።

ያም አልበቃ ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው።
ለዚያ ነው ሊቃውንት፦
"አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም።" ያሉት።

ከዚያም ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት። ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ፣ በግርፋት፣ በእሳት፣ በስለትም አሰቃየው። በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው። በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር ፳፭ ቀን አንገቱን ሰይፈውታል።

እርሱ ካረፈ በኋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኳል። አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል። ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ፪፻ ዓ/ም እንደ ተወለደ በ፪፻፳ ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ፪፻፳፭ ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል። የቅዱሱ ክብር ታላቅ ነው።

አምላከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በከበረ ቃል ኪዳኑ ይጠብቀን። ከርስቱም አያናውጠን። ከበረከቱም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሃያ አራቱ ቅዱሳን ካህናተ ሰማይ እና ቅዱስ አዝቂር ሰማዕት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ <3

እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል።

መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ።
፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።)
፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ)
፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ)
፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል)
፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል)
፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል)
፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል)
፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል)
፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል)
፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው።

ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው።
አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው።
መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው።

መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው።

ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ።

ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ።
ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ።
(ዘካ. ፩፥፲፪)
ምሥጢርን ይገልጣሉ።
(ዳን. ፱፥፳፩)
ይረዳሉ።
(ኢያ. ፭፥፲፫)
እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ።
(መዝ. ፺፥፲፩)
ያድናሉ።
(መዝ. ፴፫፥፯)
ስግደት ይገባቸዋል።
(መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰)
በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ።
(ማቴ. ፳፭፥፴፩)
በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት የሃያ አራቱን ቅዱሳን ካህናተ ሰማይን መታሰቢያ ታደርጋለች። እኒህ ቅዱሳን መላእክት በነገድ አሥር ሲሆኑ "ሱራፌል" እየተባሉ ይጠራሉ። መኖሪያቸው በኢዮር ነው። ነገር ግን ሃያ አራቱ አለቆቻቸው ተመርጠው በመሪያቸው በቅዱስ ሱራፊ አለቅነት በጽርሐ አርያም ያገለግላሉ።

በቀናች ሃይማኖት ትምህርት ሁሉም ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር ቅርብ ቢሆኑም በነጠላ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል በነገድ ደግሞ የኪሩቤል (አራቱ እንስሳ) እና የሱራፌልን (ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ) ያህል ቅርብ የለም።

ሃያ አራቱ ቅዱሳን ካህናት ሥራቸው፦
፩.እንደ ሞገድ ከአንደበታቸው ምስጋና እየወጣ ጧት ማታ ፈጣሪያቸውን ይቀድሱታል።
(ኢሳ. ፮፥፩ ፣ ራእይ ፬፥፲፩ ፤ ፭፥፲፩)
፪.የሥላሴን መንበር ያለ ማቋረጥ ያጥናሉ።
(ራእይ ፭፥፰)
፫.የሰው ልጆችን በተለይም የቅዱሳንን ጸሎት በማዕጠንታቸው ያሳርጋሉ።
(ራእይ ፰፥፫)
፬.የረከሱትን ይቀድሳሉ።
(ኢሳ. ፮፥፮)
፭.ዘወትርም ለሰው ልጆች ምሕረትን ሲለምኑ ይኖራሉ።
(ዘካ. ፩፥፲፪)

ስለ እነዚህ ቅዱሳን ካህናት (ሱራፌል) ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ብዙ ይላል።
ለምሳሌ፦ ዐቢይ ነቢይ ወልዑለ ቃል ኢሳይያስ ፈጣሪው ተቀይሞት በነበረበትና ዖዝያን በሞተበት ወራት ግሩማን ሆነው ሥላሴን "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" እያሉ ዙሪያውን ከበው ሲያመሰግኑ ሰምቷል።
ከእነርሱም አንዱ (ሱራፊ) መጥቶ በጉጠት እሳት ከንፈሩን ዳስሶ ከለምጹ አንጽቶታል።
(ኢሳ. ፮፥፩)
አቡቀለምሲስ የተባለ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ በግርማ በአምሳለ አረጋዊ ተመልክቷቸዋል። (ራእይ ፬፥፬)

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን የመሰሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ደግሞ በጣዕመ ምስጋናቸው ሲገልጿቸው፦
"ካህናተ ሰማይ ቅውማን በዐውዱ
አክሊላቲሆሙ ያወርዱ
ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ
ይርዕዱ
ከመ ኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ።" ብለዋል።
(መጽሐፈ ሰዓታት)
ትርጉሙም "በፈጣሪ መንበር ዙሪያ የሚቆሙ የሰማይ ካህናት አክሊለ ክብራቸውን አውርደው በመንበሩ ፊት ይሰግዳሉ። መብረቀ መለኮቱ በተገለጠ ጊዜም በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።" ማለት ነው። ግሩም ባሕርየ ሥላሴን ሊቋቋመው የሚችል ፍጡር የለምና።

ቅዱሳን ካህናተ ሰማይ በምስጋናቸው፣ በማዕጠንታቸውና በምልጃቸው ክቡራን ናቸውና ዘወትር ልናከብራቸው ይገባናል። የረከሰ ማንነታችንን ይቀድሱ ዘንድ፣ በምልጃቸውም ዘንድ እንድንታሰብ፣ ጸሎታችንንም ያሳርጉልን ዘንድ እንለምናቸው።

ኅዳር ፳፬ ቀን ዓመታዊ በዓላቸው ነው ማለት በየወሩ በ፳፬ ወርኀዊ በዓላቸው መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልናስባቸው ይገባል።

በተለይ ያዘነን ልብ ደስ ያሰኛሉና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጠራቸዋለን።
"ሰላም ለክሙ ካህናተ ሕጉ ወትዕዛዙ
ለእግዚአብሔር ቃል ዘጶዴሬ ሥጋ አራዙ
እምነቅዐ አፉክሙ ሐሴት ዘኢይነጽፍ ዉሒዙ
ኪያየ ኅዙነ ወትኩዘ ልብ ናዝዙ
ወበክንፍክሙ ብርሃናዊ ዐውድየ ሐውዙ።"
(አርኬ ዘኅዳር ፳፬)

<3 ቅዱስ አዝቂር ካህን <3

ከዜና ካህናት ወደ ዜና ካህናት እንለፍ። ቅዱስ አዝቂርን የመሰሉ ካህናት ምንም ሥጋ ለባሽ ቢሆኑም ሥልጣናቸውና ግብራቸው ሰማያዊ ነውና መላእክትን ይመስላሉ። አንድም በሥልጣናቸው ከመላእክት ይበልጣሉ።

"ካህናትየ ይቤሎሙ
ወእምኩሉ ፈድፋደ አክበሮሙ
ዘኢተገብረ ለመላእክት ተገብረ ለካህናት።"
ትርጉም "አገልጋዮቼ አላቸው። ከሁሉ በላይ አከበራቸው። ለመላእክት ያልተደረገ ለካህናት ተደረገ።" እንዳለ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ።
(መጽሐፈ ቅዳሴ)

ቅዱስ አዝቂርም የናግራን (የአሁኗ የመን) ክርስቲያን ሲሆን በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጹሕ የክህነት አገልግሎቱ ሰውንም ክርስቶስንም ደስ ያሰኘ አባት ነው። አሕዛብን፣ አረማውያንን ሁሉ ድል ነስቶ መንጋውን ጠብቋል፤ በቁጥርም አብዝቷል።

ገርፈው ቢያስሩት በቃሉ ሥልጣን የብረት በሮችን ከፍቶ አሕዛብን ሲያጠምቅ ተገኝቷል። ሊገድሉት ሲወስዱት በየመንገዱ ይሰብክ ነበር። ገዳዮቹ በርሃ ላይ ውኃ ጥም እንዳይገድላቸውም በአንዲት ገበታ ላይ ዝናም አዝንሞ ሰባት መቶ ወታደሮች ከነ ፈረሶቻቸው አጥግቧል።

በመጨረሻም አይሁድ በድንጋይ ሲወግሩት ድንጋዮቹ እየተመለሱ አናት አናታቸውን ብሏቸዋል። ያን ጊዜ በብስጭት አንገቱን ቆርጠውታል። አብረውም ቅዱስ ኪርያቅ ወዳጁንና አርባ ስምንት ተከታዮቹን ሰይፈዋል።

አምላከ ቅዱሳን ካህናተ ሰማይ ከምስጋናቸው ሐሴትን፣ ከማዕጠንታቸው በጐ መዓዛን ያውርድልን። በረከታቸውንም ያብዛልን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ቆርኔሌዎስ ሐዋርያዊ እና አብድዩ ነቢይ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቆርኔሌዎስ <3

ዛሬ የምንመለከተው የዚህ ቅዱስ ዜና ሕይወት በአብዛኛው የተወሰደው ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ አሥር ላይ ነው። በቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን ታሪክ ወሳኝ ከሚባሉ ክዋኔዎች የዚህ ቅዱስ አምኖ መጠመቅ ነውና በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ በስፋት ተመዝግቧል።

ምንም እንኳ ከእርሱ አስቀድሞ ኢትዮጵያዊው ባኮስ እንዳመነና እንደ ተጠመቀ ቢታወቅም (ሐዋ. ፰፥፳፮) ቅዱስ ቆርኔሌዎስ ከአሕዛብ ወገን አምኖ ሐዋርያትን የተቀላቀለ የመጀመሪያው ሰው ነው።
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
የሮም መንግሥት በቄሣሮች ሥር በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዓለምን እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ይገዛ ነበር። በየ አሕጉሩም እስከ መንደርተኛ ሹሞች ድረስ ተሹመው ግብርን ለቄሣር እየሰበሰቡ ሕዝቡን ለቄሣር ያስገዙ ነበር።

ከእነዚህ መካከልም አንዱ የሆነው ቆርኔሌዎስ በቂሣርያ ዘፍልስጥኤም (ሌላ ቂሣርያ ስላለች ነው።) የመቶ አለቃ (ሃቤ ምዕት)፣ የሠራዊት መሪ (ሊቀ ሐራ) ሆኖ ተሹሞ ነበር። የሠራዊቱን ስምም "ኢጣሊቄ" ይሉታል።

ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን አያውቅም። እንደ አረሚ (ግሪካውያን) የከዋክብት አምላኪ ነበር እንጂ። ያም ሆኖ ክፋትን የሚጠላ፣ ደግነትን የሚያበዛ፣ ምጽዋትን የሚያዘወትርና በሐቲት (በምርምር) የሚኖር ሰው ነበር።

ታዲያ በዚያ ሰሞን ክርስቶስ ኢየሱስ መድኃኒታችን የማዳን ሥራውን ፈጽሞ አበው ሐዋርያት ለትምህርተ ወንጌል እንደ ሠጋር በቅሎ ይፋጠኑ ነበር። ቆርኔሌዎስ ሹም (አለቃ) ነውና የሐዋርያት ዜና ፈጥኖ ደረሰው።

ቅዱሳኑ በስመ ክርስቶስ ድውያንን እንደሚፈውሱ፣ ሙታንን እንደሚያነሱ፣ በኃይለ መንፈስ ቅዱስም ብዙ ምልክቶችን (ተአምራትን) እንደሚያደርጉ ሰምቶ ተገረመ። እርሱ የሚያመልከው ዙሐል (የኮከብ ስም ነው።) አቅመ ቢስ ፍጡር መሆኑን ተረዳና እርግፍ አድርጐ ተወው።

ምንም የሠራዊት አለቃ (ሹም) ቢሆንም ዘወትር በመዓልትና በሌሊት ይጾምና ይጸልይ ገባ። ጸሎቱም "የእውነት አምላክ ተገለጥ።" ነበር። ጾምና ጸሎት ያለ ምጽዋት ቁም ነገር አይሠሩምና ቤቱን ቤተ-ርሑባን፣ ቤተ-ነዳያን አደረገው።

ይህ ተወዳጅ ጾም፣ ጸሎትና ምጽዋት ደግሞ ያለ ከልካይ ወደ ሰማያት፣ ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ። ምንም አሕዛባዊ (ኢ-ጥሙቅ) ቢሆንም ጌታ ግን ቅዱስ መልአኩን ላከለት።

አንድ ቀን እንዳስለመደ ሲጸልይ ዘጠኝ ሰዓት (በሠርክ) አካባቢ መልአኩ ብሩህ ልብስ ተጐናጽፎ ተገለጠለት። "ቆርኔሌዎስ ሆይ! ጸሎትህና ምጽዋትህ ወደ እግዚአብሔር ደረሰልህ። እግዚአብሔርም አሰበህ።" አለው።

"አሁንም ትድን ዘንድ በሰፋዪ ስምዖን ቤት በሃገረ ኢዮጴ ጴጥሮስ የሚሉት ስምዖን አለና እርሱን ጥራው። እርሱ የምትድንበትን ይነግርሃል።" ብሎት የምሥራቹንም ነግሮት ተሰወረው። ወዲያውም ከራእዩ የተነሳ እያደነቀ ብላቴኖቹን ጠርቶ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።

በዚያች ዕለትም የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ በቤተ ስምዖን ሰፋዪ ሳለ ይጸልይ ዘንድ ወደ ደርቡ (ፎቅ) ወጣ። በዚያም በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት። ግሩም ራእይንም ተመለከተ። "ሞጣሕት ስፍሕት" ይላታል። ከሰማይ በአራት ማዕዘን የተያዘች መጋረጃ በውስጧ የእንስሳት፣ የአራዊት፣ የአዕዋፍ ሥዕል ተስሎባት ስትወርድ ተመለከተ።

አንዲት እጅም ወደ እሪያው (አሳማ) እያመለከተች "ተንስእ ኦ ጴጥሮስ ኅርድ ዘንተ ወብላእ... - ጴጥሮስ ሆይ! ተነስ፤ ይህንንም አርደህ ብላ።" ስትለው እርሱ ግን "ግሙራ ኢቦአ ርኩስ ውስተ አፉየ - የረከሰ ነገር ከአፌ ገብቶ አያውቅም።" ብሎ መለሰ።

መልሶም "ዘእግዚአብሔር አንጽሐ አንተ ኢታስተራኩስ - እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው።" ሲለው ይህም ራእይ ሦስት ጊዜ ሲደጋገም ተመለከተ። ወዲያውም ያቺ መጋረጃ ወደ ላይ ተመለሰች።

የራእዩ ምሥጢር ለጊዜው እግዚአብሔር ከፈጠረው "ርኩስ" የሚባል እንደ ሌለ ያጠይቃል። ለፍጻሜው ግን ያቺ ሞጣሕት የወንጌል (የክርስትና) አንድም የእመ ብርሃን ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት።

እሪያው ደግሞ የቅዱስ ቆርኔሌዎስ ምሳሌ ነውና "አትጸየፈው፤ አጥምቀው።" ሲለው ነበር። ቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህ ነገር ሲያሰላስል የቅዱስ ቆርኔሌዎስ ብላቴኖች ደርሰው ጠሩት። መንፈስ ቅዱስ "አብረሃቸው ሒድ።" ብሎታልና አብሯቸው ሔደ።

ወደ ቆርኔሌዎስ ዘንድ ደርሶም ሁለቱ ራእያቸውን ተጨዋወቱ። ቆርኔሌዎስም በግንባሩ ተደፍቶ ለሊቀ ሐዋርያት ሰገደለት። ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ስለ ትሕትና "አትስገድልኝ" አለው። ከዚያም አፉን ከፍቶ ለእርሱና ለቤተሰቡ ከቅዱስ ቃሉ መገባቸው። አጥምቆም እጁን ሲጭንባቸው ከቅዱስ መንፈሱ ተካፈሉ።

ከዚህች ዕለት በኋላም ቅዱስ ቆርኔሌዎስ ሃብቱን፣ ንብረቱን፣ ሹመቱንና ክብሩን ንቆ ሐዋርያትን ተከተላቸው። ለስብከተ ወንጌል አገልግሎትም አንዲት በትር ብቻ ይዞ ወደ ምድረ ግብጽ ወረደ። በዚያም ብዙዎችን ወደ ክርስትና ስቦ ለዓመታት ተጋድሎ በዚህች ቀን ዐርፏል።

<3 ቅዱስ አብድዩ ነቢይ <3

"አብድዩ" ማለት "የእግዚአብሔር አገልጋይ" ማለት ነው። ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን የቅዱስ ኤልያስ ታላቁም ደቀ መዝሙር ነው። ቅዱሳን ነቢያት ዮናስና ኤልሳዕም ባልንጀሮቹ ነበሩ።

ቅዱስ አብድዩ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንት መቶ ዓመት አካባቢ የከሃዲው ንጉሥ የጦር መሪ ሆኖ በሃምሳ አለቃነት አገልግሏል። ግፈኛዋ ኤልዛቤል ነቢያተ እስራኤልን ስታስፈጅ ሃምሳውን በአንድ ዋሻ ሃምሳውን ደግሞ በሌላ ዋሻ አድርጐ አትርፏቸዋል። ዘጠኝ መቶው ግን ተጨፍጭፈዋል።

ያተረፋቸውንም ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ መግቧቸዋል። አክአብና ኤልዛቤል ከሞቱ በኋላም ቅዱስ ኤልያስን ተከትሎ ሹመቱን ትቷል። እግዚአብሔር ገልጾለትም ትንቢት ሲናገር ሕዝቡንም ሲገሥጽ ኑሯል።

በብሉይ ኪዳን ካሉ የትንቢት መጻሕፍትም በጣም አጭሩን የጻፈው ይህ ነቢይ ነው። ትንቢተ አብድዩ ባለ አንድ ምዕራፍ ብቻ ናትና። ቅዱሱ በዚህች ቀን ዐርፎ ወገኖቹ ቀብረውታል።

አምላከ ነቢያት ወሐዋርያት የበረከትና የሰላም ዘመንን ያምጣልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቆርኔሌዎስ (ሐዋርያዊ ጻድቅ)
፪.ቅዱስ አብድዩ ነቢይ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እስራኤል)
፬.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮.አባ ሳሙኤል
፯.አባ ስምዖን
፰.አባ ገብርኤል

"በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ በልብህም 'ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው?' የምትል አንተ ሆይ! የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን 'ከዚያ አወርድሃለሁ።' ይላል እግዚአብሔር።"
(አብድዩ ፩፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሰማዕታት ቆዝሞስና ድምያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን ቆዝሞስ ወድምያኖስ <3

እስኪ ዛሬ ስለ ክርስትናና ወጣትነት እነዚህን ቡሩካን ወንድማማች ክርስቲያኖች መሠረት አድርገን ጥቂት እንመልከት። ከዚህ በፊት የበርካታ ወጣት ሰማዕታትን ዜና ሰምተናል። መጽሐፍ እንደሚል "ወኩሉ ዘተጽሕፈ ለተግሣጸ ዚአነ ተጽሕፈ - የተጻፈው ሁሉ እኛ ልንማርበት፣ ልንገሠጽበት ነውና።" (ሮሜ. ፲፭፥፬) ልናስተውል ይገባናል።

ዜና ቅዱሳን የሚነገረን እንደ ታሪክ እንዲሁ ሰምተን እንድናልፈው አይደለም።
፩.ከልቡ ለሚሰማው (ለሚያነበው) በረከት አለው።
፪.ከቅዱሱ (ቅድስቷ) ቃል ኪዳን በእምነት ተካፋይ መሆን ይቻላል።
፫.ቅዱሳኑ ክርስትናቸውን ያጸኑበት፣ የጠበቁበትና ለሰማያዊ ክብር የበቁበትን መንገድ እንማርበታለን። ትልቁም ጥቅማችን ይሔው ነው።

ቁጥራችን ቀላል የማይባል የተዋሕዶ ልጆች ሕይወተ ቅዱሳንን እንደ ተራ ታሪክ ወይ ጀምረን እንተወዋለን። ምናልባትም በግዴለሽነት እናነበዋለን። ደስ ሲለንም ሥዕሉ ላይ 'Like' የምትለውን ተጭነን እናልፈዋለን።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በደንብ አንብበን "ወይ መታደል!" ብለን አድንቀን እናልፋለን። ማድነቃችንስ ጥሩ ነበር። ግንኮ ቅዱሳኑ ለዚህ የበቁት የታደሉ ስለ ሆኑ ብቻ አይደለም። ከእነርሱ የሚጠበቀውንም በሚገባ ሥለ ሠሩ እንጂ።

እግዚአብሔር የሚያዳላ አምላክ አይደለም። "ኩኑ ቅዱሳነ እስመ ቅዱስ አነ - እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።" (ዘሌ. ፲፱፥፪ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲፭) ብሎ የተናገረው ለጥቂት ወይም ለተለዩ ሰዎች አይደለም። በስሙ ለሚያምኑ ሁሉ ነው እንጂ።

ስለሆነም እኛ ክርስቲያኖች በተለይም ወጣቶች ከቀደምቶቻችን ተገቢውን ትምህርት ወስደን ልንጸና፣ ልንበረታ፣ ለቤተ ክርስቲያናችንም "አለሁልሽ" ልንላት ይገባል። ዛሬ እናት ቤተ ክርስቲያን በተለይ በከተሞች የወላድ መካን እየሆነች ነው።

"ይህን ያህል ሚሊየን ሰንበት ተማሪና ወጣት አላት።" ይባላል። ሲፈተሽ ግን በትክክለኛ ቦታው የሚገኘው ከመቶው ስንቱ እንደ ሆነ ለመናገርም ያሳፍራል። የሆነውስ ሆነ መፍትሔው ምንድነው ብንል እባካችሁ ከቅዱሳን ቀደምት ክርስቲያኖች መሥራት ያለብንን ቀስመን ከዘመኑ ጋር አዋሕደን (ዘመኑን ዋጅተን) ራሳችንን፣ ቤተ ክርስቲያንንና ሃገራችንን እንደግፍ። ካለንበት ያለማስተዋል አዘቅትም እንውጣ።
ለዚህም ቁርጥ ልቡና እንዲኖረን አምላካችን ይርዳን ብለን ወደ ቅዱሳኑ ዜና ሕይወት እንለፍ።

ቅዱሳን ቆዝሞስና ድምያኖስ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ በምድረ ሶርያ ተወልደው ያደጉ የዘመኑ ክርስቲያኖች ናቸው። አባታቸው በልጅነታቸው በማረፉ አምስት ወንድ ልጆችን የማሳደግ ሃላፊነት በእናታቸው ትክሻ ላይ ወደቀ። እናታቸው ቅድስት ቴዎዳዳ ትባላለች።

እጅግ የምትገርም ቡርክት እናት ናት። አምስቱ ልጆቿ "ቆዝሞስ፣ ድምያኖስ፣ አንቲቆስ፣ አብራንዮስና ዮንዲኖስ" ይባላሉ። በእርግጥ ለአንዲት እናት የመጀመሪያ ጭንቀቷ "ልጆቼ ምን ይብሉ?" ነው። ለቅድስት ቴዎዳዳ ዋናው ጉዳይ ይሔ አልነበረም።

ጌታችን እንዳስተማረን "ኢትበሉ ምንተ ንበልእ ወምንተ ንሰቲ ወምንተ ንትከደን - ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጠጨነቁ።" ብሏልና ዘወትር የምትጨነቀው ስለ ልጆቿ ሰማያዊ ዜግነት ነበር።
(ማቴ. ፮፥፴፩)

በዚህም ምክንያት አምስቱን ልጆቿን ዕለት ዕለት ወደ ቤተ እግዚአብሔር ትወስዳቸው፣ ከቅዱስ ቃሉ ታሰማቸው፣ መንፈሳዊ ሕይወትን ታለማምዳቸው ነበር። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በጐ ፈቃዳችንንና በቅንነት የሆነች ትንሽ ጥረታችንን ነውና ቅድስት ቴዎዳዳ ተሳካላት። ልጆቿ በአካልም፣ በመንፈሳዊ ሕይወትም አደጉላት።

ዘመኑ እንደ ዛሬ ተድላ ሥጋ የበዛበት ሳይሆን ክርስቲያን መሆን ለሞት የሚያበቃበት ነበር። ከዚህ በፊት እንደ ተመለከትነው ከክርስቶስ ልደት ሁለት መቶ ሰባ አምስት ዓመታት በኋላ በሶርያና በሮም የነገሡት ሁለቱ አራዊት (ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስ) ክርስቲያኖችን ከዋሉበት አላሳድሩ፣ ካደሩበትም አላውሉ አሉ።

ቀዳሚ ፈተናዋን በሚገባ የተወጣችው ቅድስት ቴዎዳዳ ይህኛውንም ትጋፈጠው ዘንድ አልፈራችም። ግን ከልጆቿ ጋር መመካከር ነበረባትና ለውይይት ተቀመጡ። ሦስቱ ልጆቿ ከልጅነታቸው ጀምረው ሲሹት የነበረውን ምናኔ መረጡ።

ቅድስቷ እናት በምርጫቸው መሠረት ቅዱሳን አንቲቆስ፣ ዮንዲኖስና አብራንዮስን መርቃ ወደ በርሃ ሸኘቻቸው። እርሷም ከሁለቱ ቅዱሳን ልጆቿ ቆዝሞስና ድምያኖስ ጋር ቀረች።

እነዚህ ቅዱሳን በከተማ የቀሩት ግን ዓለም ናፍቃቸው አይደለም። በእሥራት መከራን የሚቀበሉ የእግዚአብሔርን ቅዱሳን ያገለግሉ ዘንድ ነው እንጂ።

ቅድስት ቴዎዳዳ በቤቷ ነዳያንን ስትቀበልና ስታበላ ሁለቱ ቅዱሳን ልጆቿ ቀኑን ሙሉ እየዞሩ እሥረኞችን (ስለ ክርስቶስ የታሠሩትን) ሲጠይቁ፣ ሲያጽናኑ፣ ቁስላቸውን ሲያጥቡ አንጀታቸውንም በምግብ ሲደግፉ ይውሉ ነበር።

ይህ መልካም ሥራቸው ለፈጣሪ ደስ ቢያሰኝም አውሬው ዲዮቅልጢያኖስን ግን ከመጠን በላይ አበሳጨው። ወዲያውኑ ተይዘው እንዲቀርቡለት አዘዘ። በትዕዛዙ መሠረትም ቆዝሞስና ድምያኖስ ታሥረው ቀረቡ።

"እንዴት ብትደፍሩ ትዕዛዜን ትሽራላችሁ! አሁን ከስቃይ ሞትና ለእኔ ከመታዘዝ አንዱን ምረጡ።" አላቸው። ቅዱሳኑ ምርጫቸው ግልጽ ነበር። ከክርስቶስ ፍቅር ከቶውኑ ሊለያቸው የሚችል ኃይል አልነበረምና።
(ሮሜ. ፰፥፴፮)

ንጉሡም "ግረፏቸው" አለ። ልብሳቸውን ገፈው፣ ዘቅዝቀው አሥረው፣ በብረትና በእንጨት ዘንግ ደበደቧቸው። ደማቸውም መሬት ላይ ተንጠፈጠፈ። እነርሱ ግን ፈጣሪን ይቀድሱት ነበር።

ይህ ዜና ፈጥኖ ወደ እናታቸው ደርሶ ነበርና ቅድስት ቴዎዳዳ እየባከነች ወደ ሰማዕታት አደባባይ ሮጠች። አንዲት እናት ልጆቿ በአደባባይ ተሰቅለው ደማቸው ሲንጠፈጠፍ ስታይ ምን ሊሰማት እንደሚችል የሚያውቅ የደረሰበት ብቻ ነው።

ግን ክብራቸውን አስባ ተጽናናች። ፈጥናም በሕዝቡ መካከል ስለ ሰነፍነቱ ከሀዲውን በድፍረት ዘለፈችው። ንጉሡም በቁጣ አንገቷን በሰይፍ አስመታት። ሁለቱ ቅዱሳን ይህንን በዓይናቸው አዩ። አንዲት ነገርንም ተመኙ። የእናታቸውን አካል የሚቀብር ሰው።

ግን ደግሞ ሁሉ ስለ ፈራ የቅድስቷ አካል መሬት ላይ ወድቆ ዋለ። ያን ጊዜ ተዘቅዝቆ ሳለ ቅዱስ ቆዝሞስ አሰምቶ ጮኸ። "ከእናንተ መካከል ለዚህች ሽማግሌ ጥቂት ርኅራኄ ያለው ሰው የለም?" ሲልም አዘነ። ድንገት ግን ኃያሉ የጦር መሪ ቅዱስ ፊቅጦር ደረሰ።

ሰይፉን ታጥቆ በመካከል ገብቶ የቅድስቷን አካል አነሳ። በክብር ተሸክሞም ወስዶ ቀበራት። በመጨረሸ ግን የሦስቱ ወንድሞቻቸው ዜና በመሰማቱ ከበርሃ በወታደሮች ተይዘው መጡ። ከዚያም በብዙ መከራ አሰቃይተው በዚህች ቀን አምስቱንም አሰልፈው ገደሏቸው። የክብር ክብርንም ከእናታቸው ጋር ወረሱ።

አምላከ ሰማዕታት ከትዕግስታቸው፣ ከጽናታቸውና ከበረከታቸው ያሳትፈን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጽዮን ማርያም ማኅደረ አምላክ እና ለቅዱሳኑ ጐርጐርዮስ ወዮሐንስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጽዮን ማርያም <3

"ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው። አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው። ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘላለማዊት ርስት ያገለግላል።

እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በኋላ በጊዜው ለእስራኤላውያን ክብር፣ ሞገስ፣ አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል።
(ዘጸ. ፴፩፥፲፰)
ከዚያም ለአምስት መቶ ዓመታት ከእነርሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነርሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች።

ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ - እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጥታለች። ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን።

ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን። ግን አንጨነቅም። ምክንያቱም የመጣችውም የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም። በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም። ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም።

ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን፤ ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች። "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው። "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው።

"ታቦት" ማለት "ማኅደር - ማደሪያ" እንደ ማለት ነው። ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል። ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም ሁለት ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን። (፪ቆሮ. ፮፥፲፮ ፣ ራእይ. ፲፩፥፲፱)

በመጨረሻም ኅዳር ፳፩ ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን።
በዚህች ቀን፦
፩.ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን። ይህ ሲሆንም ቅዱስ ሙሴ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾሞ እንደ ተቀበለ ሳንዘነጋ ማለት ነው።
(ዘጸ. ፴፩፥፲፰ ፣ ዘዳ. ፱፥፲፱)

፪.በዘመነ ኤሊ ሊቀ ካህናት ታቦተ ጽዮን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ (ኢሎፍላውያን) እጅ ተማርካለች። ግን ደግሞ ዳጐንን ቀጥቅጣዋለች።
(፩ሳሙ. ፭፥፩)

፫.በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ፤ አገለገለ። ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ ተቀኘላት። በዚህም ሜልኮል ንቃው ማኅጸኗ ተዘግቷል።
(፩ዜና. ፲፭፥፳፭)
ሊቃውንትም "ድንግል እመቤታችን ማርያም በትንቢት መነጽር ተመልክቷል።" ብለውናል።
"ሰላም ለኪ ማርያም እምነ
ዘሰመይናኪ ጸወነ
ሶበ እምርሑቅ ርእየ ዘጽላሎትኪ ስነ
ለቢሶ ዳዊት ልብሰ ክብር ዘየኀይድ ዓይነ
ቅድመ ታቦተ ሕግ ኀለየ ወዓዲ ዘፈነ።" እንዲል።
(አርኬ ዘኅዳር ፳፩)

፬.በዘመነ ንጉሥ ሰሎሞን (መፍቀሬ ጥበብ) ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ ተሠርቶላት ስትገባ ታላቅ ሐሴት ተደርጓል። እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ንጉሡን አነጋግሯል።
(፪ዜና. ፭፥፩ ፣ ፩ነገ. ፰፥፩)

፭.በዚያው ዘመንም በፈጣሪ ፈቃድ ንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ (ዕብነ ሐኪም) ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል።

፮.በዘመነ አፄ ባዜን (በ፬ ዓ.ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች። በዚህ ጊዜም ሁለቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታል።

፯.በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ነገሥት ጻድቃን አብርሐ ወአጽብሐ አሥራ ሁለት መቅደሶች ያሏትን ግሩም ቤተ ክርስቲያን ለእመ ብርሃን ሠርተው በዚህች ቀን በጌታችን ተቀድሷል።

፰.በተጨማሪም በየጊዜው ማለትም በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አማካኝነት ስትፈርስ ወደ ዝዋይ ትሰደድ ነበር። ተመልሳ ስትታነጽም ቅዳሴ ቤቷ የሚከበረው ኅዳር ፳፩ ቀን ነው። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ይህ በዓል ልዩ ነው።

አማናዊት ጽዮን እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን እንዲህ እንላታለን።

"ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል። እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቡርክት እምቡሩካን፣ ኅሪት እምኅሩያን" ናትና። ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች። ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች። እርሷ እመ ብርሃን፣ የአምላክ እናቱ፣ የሰውነታችን መመኪያ ናትና።

እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት፣ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ" ማለታችን ነው።
፩."ንጽሕት" ትባላለች። ሌሎች ቅዱሳን ቢነጹ ከገቢር ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም። እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከኃልዮ ንጽሕት ናት።
"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ - ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም።" እንዲል።
(ተአምረ ማርያም)

፪."ጽንዕት" እንላታለን። ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው። እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና።
"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት።
(ቅዱስ ያሬድ)
ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም - ማርያም ዘላለማዊት ድንግል ናት።" እንዳለ።
(መጽሐፈ ቅዳሴ)

፫.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን። ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው። እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ - የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና።

፬.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን። ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል፣ እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች፣ በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን ሰማዕታት ሰርጊስ ወቴዎፍሎስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን ባኮስ ወሰርጊስ <3

ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው። ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል። ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው።

ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል። የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው። "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው።

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ። ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም።

እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ። የሚረግሟችሁን መርቁ። ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ።" ብሎናልና።
(ማቴ. ፭፥፵፬)
ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚሆንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል።

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል። የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና። እስኪ ለዛሬ ደግሞ በአጭሩ የቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስን ዜና እንካፈል።

እነዚህ ቅዱሳን የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ናቸው። ባኮስ እና ሰርጊስ (ሰርግዮስ) ከልጅነት ጀምሮ ባልንጀሮች ናቸው። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ሥር መክስምያኖስና ዲዮቅልጢያኖስ እስከ ነገሡበት ዘመን ድረስ በአንጻሩም ቢሆን ሰላም ነበር።

ታዲያ በዚህ የሰላም ጊዜ ሁለቱ ቅዱሳን ሥራ አልፈቱም። ጾምን፣ ጸሎትንና በጐ ምግባራትን ሁሉ ይከተሉ ነበር። ለመከራ ዘመን ስንቅ የሚሆነን በሰላሙ ዘመን የተያዘ ስንቅ ነውና።

በዚያው አንጻር ደግሞ ሠርቶ መብላት ይገባልና ሥራ ሲፈልጉ መክስምያኖስ ሠራዊት መሰብሰብ ጀመረ። እነርሱም ከሠራዊቱ ዘንድ ተቆጥረው የምድራዊ ንጉሥ ጭፍሮች ሆኑ። በእርግጥ በዘመናችን ለክርስትና አይመቹም ከሚባልላቸው ሥራዎች አንዱ ውትድርና ነው።

ነገር ግን ብዙ ቅዱሳንን ስትመለከቷቸው ሙያቸው ይሔው ነበር። ቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስ ጊዜው የሰላምም ይሁን የጦርነት ይጾማሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይመጸውታሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉም ዘመናት አለፉ።

ከቆይታ በኋላ ግን ሰይጣን ያደረበት ንጉሡ መክስምያኖስ ጣዖት አመለከ። አዋጅም አውጥቶ ክርስቲያኖችን ያሰቃይ፣ ይገድልም ያዘ። ቅዱሳኑ ይህንን ሲሰሙ አዘኑ።

ቁጭ ብለውም ተወያዩ። በልባቸው ፍቅረ ክርስቶስ ይነድ ነበርና ወጣትነታቸው፣ መልካቸው፣ ተወዳጅነታቸው ሁሉ ሊያታልላቸው አልቻለም። እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ስለ ሃይማኖት ሊሰው ወሰኑ።

በማግስቱም ንጉሡ ወደ ሾመው የቅርብ አለቃቸው ቀረቡና "የምንነግርህ ነገር አለን።" አሉት። "እሺ" ሲላቸው በወገባቸው ያለውን የክብር መታጠቂያና የክብር ልብሳቸውን በፊቱ ወረወሩለትና "እኛ የክርስቶስ ጭፍሮች ነንና ከዚህ በኋላ ላንተ ለጣዖት አምላኪው አንታዘዝም።" አሉት።

መኮንኑ ነዶታልና አስገረፋቸው፤ አሳሰራቸው። በረሃብና በጥም በብዙ መክፈልተ ኩነኔም አሰቃያቸው። እነርሱ ግን ጽኑዓን ነበሩና አልቻሏቸውም። ጥቅምት አራት ቀን በሆነ ጊዜ ግን ሁለቱን ለያዩዋቸው። ቅዱስ ባኮስን ለብቻው ወስደው ትልቅ ድንጋይ በአንገቱ ላይ አሠሩበትና ባሕር ውስጥ አሰጠሙት።

ነፍሱም ከሥጋው ስትለይ ባሕር ወደ ዳር አስወጣችው። በአካባቢውም "ባባ" እና "ማማ" የሚባሉ ባሕታውያን ነበሩና እግዚአብሔር እንዲገንዙት አዘዛቸው። ሲሔዱም ቅዱስ ሥጋውን አንበሳና ተኩላ ሲጠብቁት አግኝተው በታላቅ ዝማሬ ገንዘው በራሳቸው ተሸክመው ወስደው በበዓታቸው ውስጥ ቀበሩት።

ቅዱስ ሰርጊስን ደግሞ ለስድስት ቀናት ካሠሩት በኋላ እጁንና እግሩን በእንጨት ላይ ቸንክረው በእንስሳት ጭራ ላይ አስረው ሲጐትቱት ውለዋል። አንገቱን በሰየፉት ጊዜም አንዲት ወጣት ደሙን ተቀብላ በረከትን አግኝታለች። የመከራ ዘመን ካለፈ በኋላም ለቅዱሳኑ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ በዚህች ቀን ተቀድሷል፤ ተአምራትም ታይተዋል።

<3 ቅዱስ ቴዎፍሎስና ቤተሰቡ <3

ቅዱስ ቴዎፍሎስ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ሥር ይኖር የነበረ ጽኑዕ ክርስቲያን ነው። እግዚአብሔር ሲያድለው ደግሞ ጸንታ የምታጸና በርትታ የምታበረታ ሚስትን ሰጠው። ስሟም ጰጥሪቃ ይባላል።

በክርስትናዋና በፈጣሪዋ ፍቅር ላይ ይሉኝታና ድርድርን የማታውቅ ብርቱ ሴት ናት። ሁለቱ ተጋብተው በሕጉና በሥርዓቱ ሲኖሩ እግዚአብሔር በረድኤት ጐበኛቸውና ቅድስት ጰጥሪቃ ጸነሰች። በወለደችውም ጊዜ "ደማሊስ" ስትል በሃገራቸው ልሳን ስም አወጣችለት።

ልክ ግን ከአራስነት አልጋዋ በተነሳችበት ወራት ያ የመከራ ዘመን (ዘመነ ሰማዕታት) ድንገት ደረሰ። እሷም አካሏ አልጸናም፤ ልጇም ገና አምስት ወሩ ነው። ባሏ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ደግሞ በጨካኙ ንጉሥ እጅ መውደቁን (መታሠሩን) ሰማች።

ይኼ እጅግ ከባድ ፈተና ቢመስልም እርሷ ግን ልጇን አዝላ ወደ እሥር ቤት ሔደች። ባሏንም "ወንድሜ! እኔና ልጅህን በክርስቶስ ዘንድ ስለምታገኘን ጽና። ክብርህን እንዳትተው!" አለችው። እርሱም ደስ ብሎት ብዙ መከራን ተቀበለ።

ግርፋቱ፣ እሳቱ፣ ስለቱ ሁሉ ሲያልፍበት በተአምራቱ አሕዛብን ማረከ። ቅዱስ መልአክም ከሰማይ ወርዶ ማርና ወተትን መገበው። ከዚያም በዚህ ቀን ለአንበሳ ተሰጠ። አንበሳውም ለቅዱሱ ሰግዶ፣ እግሩንም ስሞ፣ አንገቱን ተጭኖ ገደለው።

ወዲያው ሚስቱ ቅድስት ጰጥሪቃ ተይዛ እርሷም ከነ ልጇ ለአንበሳ ተሰጠች። በዚህ ጊዜ የአምስት ወር ሕፃን ቅዱስ ደማሊስ አፉን ከፍቶ "እኔስ በሥላሴ አምናለሁና አንበሳን አልፈራም።" ሲል እየሳቀ ጮኸ። ወዲያውም እናትና ልጅን አንበሳው ገደላቸው። ቅዱሱ ቤተሰብም ለክብር በቃ።

አምላከ ሰማዕታት ጽንዐታቸውን፣ ትእግስታቸውንም ያድለን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሰርጊስ ሰማዕት
፪.ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሰማዕት
፫.ቅዱሳን ጰጥሪቃና ደማሊስ (የቅዱሱ ሚስትና ልጅ)
፬.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ (ልደቱ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፬.አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም
፮.ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ

"እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን።"
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. ፸፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ፣ ለቅዱስ ኤላውትሮስ እና ለደናግል አጥራስስ ወዮና ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ <3

እንደ አባቶቻችን ትርጉም 'ፊልጶስ' ማለት 'መፍቀሬ አኃው - ወንድሞችን የሚወድ' ማለት ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ነው።
(ማቴ. ፲፥፫)
በዚህ ስም የሚጠራ ሐዋርያ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ ነበር። እርሱም ጃንደረባውን ባኮስን ያጠመቀው ነው።

አንዳንዴ የሁለቱ ታሪክ ሲቀላቀል እንሰማለን። ለሁሉም ይህኛው ቅዱስ ፊልጶስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሆኖ ምሑራነ ኦሪት ከሚባሉትም አንዱ ነበር። በወቅቱ ገማልያል የሚሉት ክቡርና ምሑረ ኦሪት በርካታ ምሑራነ ኦሪትን አፍርቶ ነበር።

እንደ ምሳሌም ቅዱሳኑን "ጳውሎስን፣ ኒቆዲሞስን፣ ናትናኤልን፣ እስጢፋኖስንና ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስን" መጥቀስ እንችላለን። ቅዱስ ፊልጶስ ነገዱ ከእስራኤል ሲሆን ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ ነው። ኦሪትን ተምሮ በመንገድ ዳር ቁጭ ብሎ 'መሲሕ ቀረ' እያለ ሲተክዝ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ ደረሰ።

ትክ ብሎ አይቶት "ተከተለኝ" አለው።
(ዮሐ. ፩፥፵፬)
ቅዱስ ፊልጶስም ያለ ማመንታት ሁሉን ትቶ በመንኖ ጥሪት ተከተለው። በዚህ ዓይነት ጥሪ መድኃኒታችን ቅዱስ ማቴዎስንም ጠርቶታል። (ማቴ. ፱፥፱)
ቅዱስ ፊልጶስ ጌታን ከተከተለ በኋላ ሥራ አልፈታም። ወዲያውኑ ሒዶ ለናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) ሰበከለት እንጂ።

"ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያትም የተነበዩለትን መሲሕን አግኝቸዋለሁ።" አለው። ይህ አነጋገሩም ምሑረ ኦሪት እንደ ነበር በእርግጥ ያሳያል።
(ዮሐ. ፩፥፵፮)
ቅዱስ ናትናኤልም ምሑር ነውና "ከናዝሬት ደግ እንዴት ይወጣል?" ቢለው ቅዱስ ፊልጶስም መልሶ "ነዐ ትርአይ - ታይ ዘንድ ና።" አለው።

ናትናኤልም ሒዶ በጌታ አመነ። ቅዱስ ፊልጶስ አገልጋይ እንደ መሆኑ መጠን በዮሐንስ ወንጌል ተደጋግሞ ስሙ ተጠቅሷል። በተለይ ደግሞ ጌታ የአምስት ገበያ ሕዝብን አበርክቶ ሲመግብ አስቀድሞ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። እርሱ ግን "ጌታ ሆይ! የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ብንገዛም አንዘልቀውም።" ብሎ ነበር።

በኋላ ግን የጌታን ድንቅ ተአምር ተመለከተ። (ዮሐ. ፮፥፭)
በተለይ ደግሞ በሐዋርያት አበው መካከል ለጌታ እንደ እንደራሴ ሆኖ ያገለግል እንደ ነበርም ተጠቅሷል። ሰዎች ጌታን ማግኘት ሲፈልጉ እሱና እንድርያስን ያናግሩ ነበር።
(ዮሐ. ፲፪፥፳)
አንድ ጊዜ ግን እስካሁን ሊቃውንትን የምታስደምም ጥያቄ ጠይቆ ነበር።

አጠያየቁ ደግሞ ፍጹም የዋሕ እንደ ሆነ ያሳያል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ባሕርይ አባቱ አብ እየነገራቸው ሳለ ቅዱስ ፊልጶስ ከመካከል ተነስቶ "እግዚኦ አርእነሁ ለአብ ወየአክለነ" ልክ ወልድን በዓይኑ እንዳየ ሁሉ አብን ሊያይ ቸኩሎ "አቤቱ ስለ አብ የሰማነው ይበቃልና አሳየን?" ብሎታል።
(ዮሐ. ፲፰፥፰)

ጌታችን ግን "ዘርእየ ኪያየ ርዕዮ ለአብ - እኔን ያየ አብን አይቷል።" (ዮሐ. ፲፬፥፱) ብሎ ምሥጢረ ባሕርዩን፣ አንድነቱን ሦስትነቱን አስረድቶታል። ቅዱስ ፊልጶስም ጌታን እስከ ሕማሙ አገልግሎ፣ ቅድስት ትንሣኤውን አይቶ፣ ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ፣ ቅዱስ መንፈሱን ከሰባ ሁለት ልሳን ጋር ነስቶ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል።

ቅዱሳን ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ሲካፈሉ ለእርሱ አፍራቅያ (አፍሪካ) ደርሳዋለች። ስለዚህም በምድረ አፍሪካ ወንጌልን ከሰበኩ ሐዋርያት አንዱ ነው። በአፍራቅያና በቀድሞው የኃምስቱ አሕጉር ግዛት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጐ ብዙዎችን ወደ መንጋው (ወደ ክርስትና በረት) ቀላቀለ።

ለበርካታ ዓመታትም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተዘዋወረ ወንጌልን ሲሰብክ፣ ብርሃነ ክርስቶስን ሲያበራ፣ ነፍሳትንም ሲማርክ ቆየ። ገድለ ሐዋርያት እንደሚለው የቅዱስ ፊልጶስ ፍጻሜው በሰማዕትነት እንደ ሆነ ቢታወቅም የትኛው ሃገር ውስጥ እንደ ሆነ መለየት አልተቻለም።

ዜናው ግን እንዲህ ነው።
በአንዲት ሃገር ውስጥ ገብቶ ሰበከ፤ ብዙዎችንም አሳመነ። ያላመኑት ግን ይዘው አሰቃዩት፤ ገረፉት። "በክርስቶስ እመኑ እባካችሁ!" እያለ እየለመናቸው ዘቅዝቀው ሰቅለው ገደሉት።

ከዚያም በእሳት እናቃጥላለን ሲሉ ቅዱስ መልአክ ከእጃቸው ነጥቆ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው። በዚህ የደነገጡት ገዳዮቹ ለሦስት ቀናት ጾሙ፤ ተማለሉ። በዚህ ምክንያት የቅዱሱ ሥጋ ተመልሶላቸው ገንዘው ቀብረውት በክርስቶስ አምነዋል።

<3 ቅዱስ ኤላውትሮስ ሰማዕት <3

ቅዱሱ ሰማዕትና ቅድስት እናቱ (እንትያ ትባላለች) የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ናቸው። ቅድስት እንትያ መልካም እናት ናትና ቅዱስ ኤላውትሮስን በሃይማኖት በሥርዓት አሳደገችው። በአሥራ ሰባት ዓመቱ ዲቁናን ተሾመ። በአሥራ ስምንት ዓመቱ ቅስና፣ በሃያ ዓመቱ ደግሞ ጵጵስናን ተሾመ።

ያን ጊዜ ሃገራቸው ሮም የግፍ ቦታ ነበረችና የቅዱሱ ዜና ሕይወት፣ ብርሃንነቱ፣ ስብከቱ፣ ንጹሕ ሕይወቱ በሃገረ ገዢው ዘንድ ተሰማ። አንዱን መኮንን ጠርቶ "ሒድ አምጣው።" አለው።

መኮንኑ ሲደርስ ቅዱስ ኤላውትሮስ እየሰበከ ነበርና በጣዕመ ስብከቱ ተማርኮ ከነ ተከታዮቹ አምኖ በዚያው ቀረ። አገረ ገዢውም ሌላ መኮንን ልኮ አስመጣውና ቅዱሱን "ለምን የተሰቀለውን ታመልካለህ?" አለው።

ቅዱሱም መልሶ "ማስተዋል የተሳነህ! ቢገባህ ኑሮ የተሰቀለው እኮ ለእኔና ለአንተ ነው።" አለው። ሞት ተፈርዶበት ቅዱሱን ብዙ አሰቃይተው እሥር ቤት ሲጥሉት ርግብ መጥታ መገበችው።

እግሩን ቸንክረው በመንገድ ላይ ሲጐትቱት መልአክ ወርዶ ፈታው። ወደ በርሃም ወሰደው። ከጊዜያት በኋላ እንደ ገና ይዘው አምጥተው ብዙ አሰቃይተው በዚህች ዕለት ከእናቱ ቅድስት እንትያ ጋር በጦር እየወጉ ገድለዋቸዋል።

ሊቃውንትም የሰማዕታቱንና የሐዋርያውን ተጋድሎ እያደነቁ እንዲህ ጸልየዋል፦
"ሰላም ለፊልጶስ ጽዑረ አባል በመቅሰፍት
ወለኤላውትሮስ ርጉዝ በብልኃ ኩናት
ምስለ እንትያ እባእ ኀበ ተርኅወ ገነት
ያሩጸኒ መዓዛሆሙ ወጼናሆሙ ዕፍረት
ለዝ ሐዋርያ ወለዝ ሰማዕት።"
(አርኬ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዓለም ሁሉ መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እና ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ <3

ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ፣ ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሐ ስለ እርሱ ሊናገር አይቻለውምና። አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል። እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ነገዱ ከሶርያ ሲሆን የተወለደው በ፫፻፵፯ ዓ.ም በእስክንድርያ ነው። አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ። እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው። ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምህርትና በጥበብ አደገ። ገና በሕፃንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው። በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በአሥራ አምስት ዓመቱ ነበር። በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው።

ቅዱሱ ገና በአሥራ ስድስት ዓመቱ ሃብት፣ ንብረት፣ ውበት፣ ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ። ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ እርሱ መጡ። ሊቀ ሐዋርያት የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ ሥልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት።

ከዚህች ዕለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምሥጢራት ሆነ። ብሉይ ከሐዲስ፣ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራእየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጓሜ ተነተናቸው። በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው። ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት መልእክታትና ትርጓሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ። በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ ማዕርጉም ዲቁና ነበር።

ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ። በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት። አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም። ከጣዕመ ትምህርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር። ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር። አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል አፈ ወርቅ ብላ ጠርታዋለች። ለዚያም ነው አፈ ወርቅ የሚባለው። ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልአከ ሞትን ገስጾ አሥር ዓመት አቁሞታል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም። በእርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው። ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር። ምክንያቱም የወቅቱ ንግሥት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት። እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ ሁለት ጊዜ አጋዘችው። በተሰደደበት ሃገር ፍሬ አፍርቶ፣ አስተምሮና አሳምኖ በ፬፻፯ ዓ.ም ዐርፏል። ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በስልሳ ዓመቱ አጡት። በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ።

አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ፤ (ግብዣ አዘጋጀ።) በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ እነ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ።

ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ?" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን። እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና።" አሉት። "እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንዲገለጥልኝ መርቁኝ።" አላቸው። ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ።

በማግስቱ በቤተ መንግሥት ውስጥ ሊቃውንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ጳጳሳቱ፣ ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም። ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ?" ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው።

"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ - የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም።' (ማቴ. ፩፥፳፭) ማለቱ ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር።

"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች። ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል። እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር። 'እርሷ ማን ናት? በማኅጸኗ ያለውስ ማን ነው?' እያለ ይጨነቅ ነበር። ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና። አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም። አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ ልጇም አምላክ ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው።" እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ በዚያ የነበረች ሥዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች።

ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በሥዕሏ ላይ አደረገ። አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ..... " ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት። ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል።

ሊቁ ባረፈ በሠላሳ አምስት ዓመቱ በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን በዚህች ቀን ሥጋው ፈልሷል። ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት የተነሳ ታላቅ ዝማሬና እንባ ተደርጓል። አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን ባርኳል።

ቅዱሱ ሲጠራ እንዲህ ነው፦
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣
አፈ በረከት፣
አፈ መዐር (ማር)፣
አፈ ሶከር (ስኳር)፣
አፈ አፈው (ሽቱ)፣
ልሳነ ወርቅ፣
የዓለም ሁሉ መምህር፣
ርዕሰ ሊቃውንት፣
ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)፣
ሐዲስ ዳንኤል፣
ሊቀ ጳጳሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)፣
መምህር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ፣
ጥዑመ ቃል.....

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅዱሳን አኖሬዎስ ንጉሥ፣ አባ ዳንኤል፣ ቅድስት ጣጡስ ወአባ አቡናፍር ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ አኖሬዎስ ወአባ ዳንኤል <3

አኖሬዎስ የሚለው ስም በቤተ ክርስቲያን እጅግ ተወዳጅ ነው። በሃገራችንና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናትም ብዙ ቅዱሳን በዚህ ስም ተጠርተዋል። ቅድሚያውን ግን ቅዱሱ ንጉሥ አኖሬዎስ ይወስዳል።

ቅዱስ አኖሬዎስ ተወልዶ ያደገው በሮም ከተማ ሲሆን የደጉ ንጉሥ ዐቢይ ቴዎዶስዮስና የመርኬዛ ልጅ ነው። ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ሙሽራው እና ደጉ አርቃዴዎስ ወንድሞቹ፣ ጻድቁ አቡነ ኪሮስ ደግሞ አጐቱ ናቸው። በልጅነቱ ክርስትናን የተማረው ከታላቁ ቅዱስ አርሳኒ ነው።

ምንም በቤተ መንግሥት ውስጥ ቢያድግም ቅዱስ አርሳኒ እንደ ተራ ሰው እየገረፈና እየቀጣ አሳድጐታል። ቴዎዶስዮስ ቄሣር (አባቱ) ባረፈ ጊዜ የሮም ግዛትን በስምምነት ከወንድሙ አርቃዴዎስ ጋር ተካፈሉ። በ፫፻፺ዎቹ አካባቢም አኖሬዎስ በሮም፣ አርቃዴዎስ በቁስጥንጥንያ ነገሡ።

ቅዱስ አኖሬዎስ ይህንን ዓለም አልፈለገውምና ወደ ገዳም ልኮ አንድ ባሕታዊ (አባ አውሎጊስ ይባላል።) አስመጥቶ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸመ። አክሊለ ሦኩንም በወርቅ ዘውዱ ውስጥ አደረገው።

ልብሰ ምንኩስናውን በሰንሰለት በውስጥ አሥሮ በላዩ ላይ የመንግሥቱን ካባ ደረበ። ቀን ቀን እንደ ንጉሠ ነገሥት ሲፈርድ፣ ሲተች፣ የተበደለ ሲያስክስ፣ የተቀማ ሲያስመልስ ይውል ነበር።

ሌሊት ደግሞ ባጭር ታጥቆ ሲወድቅ ሲነሳ፣ ሲጸልይ ሲሰግድ፣ ያለ ዕረፍት ያድራል። መቼም ቢሆን ከደረቅ ቂጣ፣ ከጨውና ከጥሬ ጐመን በቀር ሌላ ምግብን አይቀምስም። ይኸውንም ጾሞ ውሎ ማታ ብቻ ይመገብ ነበር።

ይህንንም ሲያደርግ ሰሌን ሰፍቶ፣ ያንን አሽጦ እንጂ በሌሎች ገንዘብ አልነበረም። ሰዎች እንዳይጠረጥሩትም "በእልፍኙ ውስጥ ሚስት አለችው።" እያለ ያስወራ ነበር። በዚያ ላይ መልኩ ያማረ ስለ ነበር በዚህ የጠረጠረው የለም። በዚህ መንገድ ከአባ አውሎጊስና ከደቀ መዝሙሩ ጋር ሆኖ ለአርባ ዓመታት ተጋደለ።

በአራተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በአምስተኛው መጀመሪያ በግብጽ ውስጥ ከነበሩ ከዋክብት አንዱ አባ ዳንኤል ሲሆን መንኖ ገዳም ከገባባት ቀን ጀምሮ በፍጹም ተጸምዶ፣ ከእህል ተከልክሎ፣ ቅጠል እየበላ ለአርባ ዓመታት ተጋደለ። አንድ ቀን ግን ተፈተነ። በትዕቢት "ከእኔ የሚበልጥ ማን አለ?" ሲል በማሰቡ ፈጣሪ መልአኩን ልኮ ገሰጸው።

ቀጥሎም "ሒድና ንጉሡን አኖሬዎስን እየው። እርሱ ንጉሥ ቢሆንም በቅድስና ይተካከልሃል።" አለው። አባ ዳንኤልም በደመና ወደ ሮም ሒዶ ቅዱሱን ንጉሥ ተገናኘው። ቅድስናውን ዐይቶም ለቅዱስ አኖሬዎስ ሰገደለት። እያለቀሰም ወደ በዓቱ ተመለሰ።

ቅዱስ አኖሬዎስ ግን ከመምህሩ ቅዱስ አውሎጊስና ከደቀ መዝሙሩ ጋር መንግሥቱን ትቶ ጠፍቶ በርሃ ገብቶ ከአባ ዳንኤል ጋር ተቀመጠ። ከተጋድሎ በኋላም አራቱም ቅዱሳን በዚህች ቀን ዐርፈዋል።

<3 ቅድስት ጣጡስ ሰማዕት <3

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደዚህች ቅድስት ወጣት መልከ መልካም አልነበረም። ቅድስት ጣጡስ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በዘመነ ሰማዕታት) የነበረች ሮማዊት ክርስቲያን ስትሆን መልኳን ያየ ሁሉ ይደነቅ፣ ይደነግጥም ነበር።

እርሷ ግን ለወንድሞቿ እንቅፋት እንዳትሆን በፊቷ ላይ ዓይነ ርግብ ጣል አድርጋና እንደ ነገሩ ለብሳ ትኖር ነበር። (እንዲህ ነበሩ እናቶቻችን!) ታዲያ በዘመኑ እስክንድሮስ የሚባል አረማዊ "ለጣዖት ስገዱ።" እያለ ክርስቲያኖችን ሲገድል የእርሷ ተራ ደረሰ።

በዐውደ ስምዕ (በምስክርነት አደባባይ) ላይ አቁሟት "ፊቷን ግለጡልኝ።" አለ። ቢገልጧት ከመልኳ ማማር የተነሳ ፈዘዘ። እጅግ በመፍጠንም "ላግባሽ?" አላት። "ሙሽርነቴ ሰማያዊ ነውና አይሆንም!" አለችው። ለመናት አልሰማችውም። አስፈራራት አልደነገጠችም።

ከዚያ ግን አስገረፋት። ከአካሏም ስለ ደም ፈንታ ወተት ፈሰሰ። ተበሳጭቶ ለአራዊት ጣላት። እነርሱ ግን ሰገዱላት። በእሳትም ፈተናት። እርሷ ሁሉንም ታግሣ ጸናች። በመጨረሻው ግን በዚህች ቀን አስገደላት። ፈጣሪዋ ክርስቶስም በሰማያዊ አክሊል ከለላት።

<3 ቅዱስ አቡናፍር ገዳማዊ <3

ጻድቁ ተወልዶ ያደገው በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ነው። ወቅቱ ሥርዓተ መነኮሳት የሚጠበቅበት፣ አበው ባሕታውያን እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝተው የደመቁበት ነበር።

ታላቁ አቡናፍርም ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ፣ በሥርዓት አድጎ፣ መጻሕፍትንም ተምሮ ገና በወጣትነቱ መንኗል። ሥርዓተ መነኮሳትን ከአባ ኤስድሮስ ታላቁ አጥንቶ ገዳሙንና መምህሩን እየረዳ ለብዙ ዓመታት በጾምና በጸሎት ኑሯል።

መነኮሳቱ ስለ ትሕትናውና ስለ ታዛዥነቱ ፈጽመው ያከብሩት ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋውያን መነኮሳት ጭው ባለ በርሃ ስለሚኖሩ ባሕታውያን ሲጨዋወቱ፣ ሲያደንቋቸውም ሰማ።

እርሱ በዚያ ወቅት ባሕታውያን በበርሃ መኖራቸውን አያውቅም ነበርና ሒዶ መምህሩን አባ ኤስድሮስን ጠየቃቸው። እርሳቸውም "አዎ ልጄ! ከዚህ በጣም ርቅው፣ ንጽሕናቸውን ጠብቀው፣ ከሰውና ከኃጢአት ተለይተው የሚኖሩ ገዳማውያን አሉ።" አሉት።

ቅዱስ አቡናፍር "በዚህ ካሉት መነኮሳትና በበርሃ ካሉት ማን ይበልጣል?" ቢላቸው "እነርሱ በጣም ይበልጣሉ። ዓለም እንኳ ከነ ክብሯ የእግራቸውን ሰኮና አታህልም።" አሉት። ይህንን የሰማው ቅዱስ አባ አቡናፍር ጊዜ አላጠፋም፤ ከመምህሩ ቡራኬ ተቀብሎ ወደ በርሃ ሔደ። ለብዙ ቀናት ከተጓዘ በኋላ አንድ ባሕታዊ አግኝቶ አብሯቸው ተቀመጠ። ከእርሳቸው ዘንድም ሥርዓተ ባሕታውያንን ተምሮ እንደገና ወደ ዋናው በርሃ ጉዞውን ቀጠለ።

ከብዙ ቀናት መንገድ በኋላም አንድ ሠፊ ሜዳ ላይ ደረሰ። አካባቢው የውኃ ጠብታ የማይገኝበት ይቅርና መጠለያ ዛፍ የሣር ዘር እንኳ የሌለበት ወይም በልሳነ አበው "ዋዕየ ፀሐይ የጸናበት፣ ልምላሜ ሣዕር የሌለበት፣ ነቅዐ ማይ የማይገኝበት" ቦታ ነበር። በዚህ ቦታ ይቅርና የሰው ልጅ አራዊትም አይኖሩበትም።

ለአባ አቡናፍር ግን ተመራጭ ቦታ ነበር። ቅዱሳኑን ይህ አያሳስባቸውም። ምክንያቱም ለእነርሱ ምግባቸውም፣ ልብሳቸውም ፍቅረ ክርስቶስ ነውና።

አባ አቡናፍር ወደ ፈጣሪ ጸለዩ። በእግዚአብሔር ቸርነት ከጎናቸው አንዲት ዘንባባ (በቀልት) በቀለች። ከእግራቸው ሥርም ጽሩይ ማይ (ንጹሕ ምንጭ) ፈለቀች።

ጻድቁ ተጋድሏቸውን ቀጠሉ፤ ዓመታት አለፉ። ልብሳቸውን ፀሐይና ብርድ ጨርሶት ቅጠል ለበሱ። በዚያ ቦታም የሰው ዘርን ሳያዩ ለስልሳ ዓመታት በተጋድሎ ኖሩ። የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አባ በፍኑትዮስን (የባሕታውያንን ዜና የጻፈ አባት ነው።) ላከላቸው።

ቃለ እግዚአብሔርን እየተጨዋወቱ ሳለ የአባ አቡናፍር አካሉ ተለወጠ፤ እንደ እሳትም ነደደ። አባ በፍኑትዮስም ደነገጠ። ታላቁ ገዳማዊ ግን እጆቻቸውን ዘርግተው ጸለዩ፣ ሰገዱና አማተቡ። ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በዝማሬና በማኅሌት አሳረጓት። የሚገርመው ደግሞ አባ በፍኑትዮስ ይህን ሲያይ ቆይቶ ዘወር ቢል ዛፏ ወድቃለች፤ ምንጯም ደርቃለች።

አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን ክብሩን፣ አእምሮውን፣ ለብዎውን ያሳድርብን። ከወዳጆቹ በረከትም ያሳትፈን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጾመ ነቢያት፣ ቅዱስ ሚናስ እና ቅዱስ ቂርቆስ ሕፃን ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ጾመ ነቢያት <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው ሰባት አጽዋማት አሏት። "ጾም" ማለት "መከልከል" ነው። የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ መባልዕት መከልከልን ይመለከታል።

"ሰባቱ" አጽዋማት፦
፩.ዓቢይ ጾም
፪.ጾመ ፍልሠታ
፫.ጾመ ሐዋርያት
፬.ጾመ ነቢያት
፭.ጾመ ድኅነት
፮.ጾመ ነነዌ እና
፯.ጾመ ገሃድ ይሰኛሉ።

በእነዚህ አጽዋማት ከዓቢይ ጾም በቀር እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ መጾም ይገባል። ዓቢይ ጾም ግን የተለየ ሥርዓት አለውና ይቆየን። ስለ ጾም ሲነሳ አስቀድሞ የሚመጣው ጥያቄ አስፈላጊነቱ ነው። "ጾም ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ ከመጠየቅ "ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ መጠየቁ ይቀላል።

ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ትዕዛዛት ትልቁ በመሆኑ እርሱን መቃወም ሃይማኖትንና አዛዡን እግዚአብሔርን መቃወም ነውና። እኛ ሃገር ላይ የተለመደች ክፉ ልማድ አለች። የከበደችንን ነገር "አያስፈልግም" በሚል እንከራከራለን።

ደግሞ ጾምን ለመሻር ጥቅስ የሚጠቅሱ ወገኖች በጣም ይገርሙኛል። ኃጢአትን ለመሥራት፣ ጾምንም ለመሻር ጥቅስን መጥቀስ አያስፈልግም። እኛ ግን ከፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ (ማቴ. ፬፥፪) አበው ቅዱሳን ጾመው (ዘዳ. ፱፥፲፱ ፣ ፩ነገ. ፲፱፥፰ ፣ ሐዋ. ፲፫፥፫ ፩ቆሮ. ፬፥፲፩) አሳይተውናልና እንደ አቅማችን እንጾማለን።

ጾመ ነቢያት ማለት ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው። በተለይ አባታችን አዳም፣ ቅዱስ ሙሴ፣ ቅዱስ ኤልያስና ቅዱስ ዳንኤል በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው።
(ዘዳ. ፱፥፲፱ ፣ ፩ነገ. ፲፱፥፰ ፣ ዳን. ፱፥፫)

ቅዱስ ዳዊት "ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ" (መዝ. ፷፰፥፲ ፤ ፻፰፥፳፬) ብሎ ዘወትር ሰውነቱን በምን ለእግዚአብሔር ያስገዛ እንደ ነበር ጠቅሷል። ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል፤ ለሞትም አብቅቶታል።

በየዘመኑ ጻድቃነ ብሊት በጾማቸው ከመዓት ርቀዋል። ጸጋ፣ ክብርና ሞገስንም አግኝተዋል። ይህ ጾም ኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን የሚጠናቀቅ ሲሆን በአራት ዓመት አንዴ አንድ ቀን ወደ ኋላ ያሰግራል።

ጾሙም የተለያዩ መጠሪያዎች ሲኖሩት እነዚህ ይጠቀሳሉ፦
፩.ጾመ ነቢያት
፪.ጾመ ማርያም (ጌታን ጸንሳ ሳለ የአባቶቿን ጾም ጾማለችና።)
፫.ጾመ ሐዋርያት (ሐዋርያትም በረከተ ነቢያትን ሲሹ ይጾሙት ነበርና።)
፬.ጾመ ጌና ("ጌና - ልደተ እግዚእ ስቡሕ" ማለት ነው።)
፭.ጾመ ስብከት (ስብከተ ነቢያት ስለሚታሰብበት)
፮.ኅዳር ጾም (በወሩ ምክንያት)
፯.ጾመ ፊልጶስ (አርድእተ ፊልጶስ ሐዋርያ ለጉዳይ ስለ ጾሙት።)

አምላከ አበው ነቢያት በጾሙ ከሚገኘው ጸጋ በረከት አይለየን።

<3 ቅዱስ ሚናስ ምዕመን ሰማዕት <3

ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) በምድረ ግብጽ ተወዳጅ ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው ነው። ልክ በሃገራችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዩ ቦታ እንዳለው ሁሉ ግብጻውያን ማር ሚናስን ጠርተው አይጠግቡትም።

ምክንያቱም ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ በመሆኑና ዛሬም ድረስ ለጆሮና ለዓይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ስለሚሠራ ነው። በተለይ ለታመመ፣ ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ ደራሽ፣ ባለ በጐ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ ነው።

"ግብጽ ውስጥ ቅዱሱን የማያውቅ ሰው ካገኛችሁ እርሱ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም ማለት ነው።" ሲባልም ሰምተናል። በነገራችን ላይ ለቅዱሳን ተገቢውን ክብር በመስጠት፣ ታሪካቸውን በመጻፍ፣ በማጥናት፣ በመጽሔት፣ በፊልምና በመሳሰሉት ለሕዝብ በማስተዋወቅ ግብጻውያኑ ከእኛ ብዙ ርቀት ሒደዋል። ዛሬ እንኳ የምንጠቀምበትን ስንክሳር ሰማንያ ከመቶ እጁን ያዘጋጁት እነርሱ ናቸው።

አባቶቻችንና እናቶቻችን ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ግን አብዛኞቹ ተረስተው ቀርተዋል። መጽሐፈ ገድላቸውንም ብል በልቶታል። ዛሬም የቤት ሥራው የእኛ ብቻ ነው።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ ሚናስ ትርጉሙ ታማኝና ቡሩክ ማለት ነው።
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ የደጋግ ክርስቲያኖች ልጅ።
በልጅነቱ የቅድስና ሕይወትን ያጣጣመ።
በዘመኑ ሰው እጅግ ተወዳጅ የነበረ።
ሃብትን፣ ክብርን፣ ሥልጣንን ንቆ በጾምና በጸሎት የተወሰነ።
በመጨረሻም በክርስቶስ ስላመነ አላውያን የገደሉት ሰማዕት ነው።

እርሱ ሰማዕት ከሆነ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ምዕመናን ክቡር አካሉን ፈልገው ያጡታል። የሚገለጥበት ጊዜ ሲደርስ ግን እርሱ የተቀበረበት ምድረ በዳ የበጐችና የእረኞች መዋያ ነበርና ተአምራትን አደረገ።

አንድ እረኛ በጐቹ ድውያን ሆኑበት። በዚያ ሰሞን ከቅዱሱ መቃብር ላይ ጠበል ፈልቆ ነበርና እረኛው ተርታ ውኃ ነው ብሎ በጎቹን ሲያጠጣቸው አንዱ ድውይ በግ ወደ ጠበሉ በመዘፈቁ ዳነ።

በዚህ የተገረመው እረኛ ሁሉንም የታመሙ በጐቹን አምጥቶ ነከራቸው፤ እነርሱም ተፈወሱ። ይህ ዜና በምድረ ግብጽ ሲሰማ ድውያን ሁሉ እየመጡ ይፈወሱ ገቡ። ግን እነሱም ሆነ እረኛው ምክንያቱን ማወቅ አልቻሉም። ነገሩ በሮም ንጉሥ ዘንድ ሲሰማ ሴት ልጁን ከሠራዊቱ ጋር ላካት።
ምክንያቱም እርሷ ከብዙ ዘመን ጀምራ መጻጉዕ ነበረችና ፈውስን አጥታ ነበር።

መጥታ ተጠመቀች፤ ፈጥናም ተፈወሰች። እርሷ ግን እንደ ሌሎች ያዳናትን ማንነት ሳታውቅ መሔድ አልፈለገችምና ሱባዔ ገባች። ቅዱስ ሚናስ በሌሊት ራዕይ መጥቶ ሥጋው እንዳለ ነገራት። እርሷም መሬቱን አስቆፍራ የቅዱሱን አካል በክብር አስወጣች።

ከዚያም በንጉሡ ትዕዛዝ ምድረ በዳው ከተማ እንዲሆን ተቀየረ። ስሙም "መርዩጥ" ተባለ። ጠበሉ የነበረበት ቦታም ላይ የማር ሚናስ ቤተ ክርስቲያን ታንጾበት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል።

<3 ቅዱስ ቂርቆስ ሕፃን <3

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው። በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው።
ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦
"መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል።"
(ማቴ. ፯፥፲፯)

መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብፁዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል። ቡርክተ ማኅጸንም እንላታለን። የተባረከ ማኅጸኗ የተባረከ ልጅን ለዘጠኝ ወር ተሸክሟልና።

በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕፃን እርሷን መስሎ እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና። አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዚህች ቀን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብጹዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች።

ፈጣሪ ቢያቆየን የሰማዕትነት ዜናቸውን ጥር ፲፭ ቀን የምንመለከት ነንና የዚያ ሰው እንዲለን እንማጸነዋለን።

አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን። በይቅርታው ኃጢአታችን ይተውልን። ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አባ ዳንኤል ወአባ መርትያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አባ ዳንኤል ገዳማዊ <3

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ በፋርስ (የአሁኗ ኢራን) ውስጥ ብዙ አስቸጋሪ ነገሥታት ተነስተው ነበር። ከእነዚህ አንዱ የሆነው የዘመኑ መሪ ክርስቶስን የማያውቅ፣ መምለኬ ጣኦት የሆነና በጠንቅ ዋዮች ተከቦ የሚኖር ነበር።

እግዚአብሔር ለሁሉም የጥሪ ቀን አለውና ለሕይወት ይጠራው ዘንድ ይህንን ንጉሥ በደዌ ጐበኘው። የአምላክ ጥሪው አንዳንዴ እንደዚህ አንዳንዴም እንዲያ ነውና። ንጉሡ እንደ ታመመ ጠቢባነ ፋርስ ሊያድኑት ሞከሩ፤ ግን አልቻሉም። ሕመሙ እየባሰ ሒዶ ንጉሡ መጻጉዕ ሆነ።

በጊዜው ከመተተኞች ሁሉ በጣም የሚያቀርበው አንድ ጠንቅ ዋይ በቤተ መንግሥት አካባቢ ነበርና ንጉሡ አስጠርቶ "አድነኝ" አለው። እንደማይችለው ሲያውቅ ዝም አለው። ንጉሡ መልሶ "ስማ! በቤቴ ውስጥ ከብረህ፣ ገነህ፣ የበላሁትን በልተህ፣ የጠጣሁትን ጠጥተህ የምትኖረው ለዚህ ላትሆነኝ ነው?" ብሎ ተቆጣው።

የንጉሡን ቁጣ ያየው መተተኛ እንደሚገድለው ባወቀ ጊዜ "ንጉሥ ሆይ! እኔኮ አታደርገውም ብዬ ነው እንጂ መድኃኒቱን አውቀዋለሁ። "ኅሥሥ ሕፃነ ዘዋሕድ ለአቡሁ ወእሙ - ለእናት አባቱ አንድ የሆነ ሕፃን ፈልግ። እናቱ አስራው አባቱ ይረደውና በደሙ ታጥበህ ትድናለህ።" አለው።

መተተኛው እንዲህ ያለው "ሲሆን ንጉሡ እንዲህ አያደርግም። ካልሆነ ግን እንዲህ ዓይነት ወላጆች አይገኙም።" ብሎ ነው። ንጉሥ ግን ላስፈልግ ባለ ጊዜ የሚያጣው ነገር የለምና አንድ ልጅ ብቻ ያላቸው ርጉማን ወላጆችን አገኘ።

"አንድ ሺህ ወቄት ወርቅ ልስጣችሁ እና ልጃችሁን ሰውልኝ።" ቢላቸው "እሺ" ብለው ወደ ንጉሡ አደባባይ ወጡ። በዚያም ሕዝብ ተሰብስቦ ንጉሡም በዙፋኑ ተቀምጦ ሳለ የአምስት ዓመት ሕፃን ልጃቸውን ለገንዘብ ይሰውት ዘንድ ወላጆቹ ቀረቡ። እናቱ አጥብቃ አሰረችው። አባቱ ደግሞ ቢላውን አስሎ ቀረበ።

በዚያች ሰዓት ግን ሕፃኑ ወደ ሰማይ ዓይኑን አቅንቶ እንባው እየፈሰሰ ሲጸልይ ከንፈሮቹ ይንቀሳቀሱ ነበርና ንጉሡ ተመልክቶ ልቡ ራራ። "እንዳትነኩት!" ሲልም ጮኾ ተናገረ። "ፍቱት" ብሎ ሕፃኑን አስፈትቶ በዙፋኑ ፊት ጠየቀው።

"ምን እያደረክ ነበር?" ቢለው "ለሕፃን ልጅ ጋሻዎቹ ወላጆቹ ናቸው። በደል ሲያገኘኝ ወደ ወላጆቼ እንዳልጮህ ገዳዮቼ እነሱው ናቸው። ወደ ዳኛም አቤት እንዳልል አስገዳዩ ዳኛው ራሱ ነው። ስለዚህም ተስፋዬ አንዱ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነበርና ወደ እርሱ በልቤ ጮህኩ።" ሲል መለሰለት። በዚህ የተገረመው ንጉሡ አንድ ሺህ ወቄት ወርቁን ከወላጆቹ ቀምቶ ለሕፃኑ ሰጥቶ በሰላም አሰናበተው።

ራርቶ ሕፃኑን የፈታው ንጉሥ ሕመሙ ቢጠናበት "የዚህ ሕፃን አምላክ እኔንም እርዳኝ!" ሲል ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጩኸቱ ወደ መንበረ ጸባኦት ደረሰለት። የእግዚአብሔር ድምጽም ወደ ታላቁ ገዳማዊ ሰው ወደ አባ ዳንኤል መጣ። "ሒደህ ፈውሰው።" አለው።

አባ ዳንኤል ማለት በዘመኑ ከነበሩ ዓበይት ጻድቃን አንዱ ሲሆን መንኖ በርሃ ከገባባት ቀን ጀምሮ በፍጹም ተጸምዶ፣ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት የኖረ አባት ነው። በዚያች ሰዓትም ጻድቁ በደመና ተጭኖ ከበርሃ ብሔረ ፋርስ ደረሰ። ከንጉሡም ጋር ተነጋገረ።

ንጉሡ "አድነኝ?" ቢለው "እንድትድን በእውነተኛው አምላክ ማመን አለብህ።" አለው። "ክርስቶስ አምላክ መሆኑን በምን አውቃለሁ?" ብሎ በመጠየቁ ጻድቁ በፊቱ ብዙ ተአምራትን በስመ ክርስቶስ አደረገለት።

ንጉሡም በክርስቶስ አምኖ በተጠመቀ ሰዓት አካሉ ታድሶ ከደዌው ድኖ ተነሳ። ሠራዊቱና ሕዝቡም እንዲሁ ተጠመቁ። አባ ዳንኤልም በደመና ወደ በርሃ ተመልሶ ከተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል።

<3 አባ መርትያኖስ <3

ይህ ቅዱስ ሰው የነበረው በዚያው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን በትውልዱ ሶርያዊ ነው። ብዙ ጊዜም "መርትያኖስ ካልዕ" (ሁለተኛው) እየተባለ ይጠራል። ምክንያቱም ቀዳማዊ መርትያኖስ (ታላቁ) ስላሉ ነው።

አባ መርትያኖስ በምድረ ሶርያ ከክርስቲያን ወላጆቹ ጋር አድጐ፣ የቀናውን የሃይማኖት ትምህርት ተምሮ፣ በጐውን ጐዳና መርጧል። ወቅቱ አርዮሳውያን የበዙበት በመሆኑ ወገኖቹን ይጠቅም ዘንድ ያስተምር ነበር።

በየሥፍራውም እየሔደ ውሉደ አርዮስ (መናፍቃንን) እየተከራከረ ምላሽ ያሳጣቸው ነበር። በዚህ የተበሳጩ መናፍቃንም አንድ ቀን አሳቻ መንገድ ላይ ጠብቀው በበትር ደበደቡት። በሞትና በሕይወት መካከልም ትተውት ሔዱ። እነርሱ በዚህ እናስተወዋለን መስሏቸው ነበር።

እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ድኖ እንደ ገና በሰው ፊት ምላሽ አሳጥቶ አሳፈራቸው። እነርሱም መንገድ ላይ ጠብቀው እየደበደቡ ጐተቱት። ለብዙ ጊዜም ሲደበድቡት ወደ በርሃ ሸሸ። በዚያም ገዳማዊ ሰው ሆኖ በጾምና በጸሎት ኖረ። በዓቱንም በኤርትራ ባሕር ዳርቻ አካባቢ ባለች አንዲት በርሃ አደረገ።

እግዚአብሔር ግን ይህንን ሐዋርያዊ ሰው ይፈልገዋልና እንደ ገና ወደ ከተማ የሚመለስበትን ምክንያት ፈጠረ። በዘመኑ የሃገሩ ጠራክያ ጳጳስ ዐርፎ "ማንን እንሹም?" ብለው ሲጨነቁ ፈጣሪ ጻድቁን በኅሊናቸው ሳለባቸው። እንደ ምንም ብለው ፈልገው አገኙትና አሥረው አምጥተው የጠራክያ ኤጲስ ቆጶስ አደረጉት።

አሁን ስብከተ ወንጌል ሠመረ። ምክንያቱም አርዮሳውያኑ እርሱ የመንጋው እረኛ ነውና መንካት አይችሉም። ቢያደርጉትም እጅግ ተወዳጅ ስለ ሆነ ጠቡ ከሕዝብ ጋር ነው። በዚሁ መንገድ አባ መርትያኖስ ተጋድሎውን ሳይገታ በሠመረ ስብከቱ ብዙዎችን አሳምኖ ወደ መንጋው ቀላቀለ።

ከሠራቸው ብዙ ተአምራትም አንዱን እነሆ፦
አንዴ ቅዱሱ መንገድ ሲሔድ ጭቅጭቅ ሰምቶ ቀረበ። በቦታው የተጋደመ ሬሳ አለ። "ምንድን ነው ችግሩ?" ቢላቸው የሟች ወገኖች ወደ አንድ ጐረምሳ እየጠቆሙ "አላስቀብር አለን።" አሉት።

ያንን ጐረምሳ "ለምን?" ቢለው "ብድር ነበረበትና ካልከፈሉኝ አይቀበርም።" አለው። ጻድቁ ፈጣሪውን ጠይቆ ጐረምሳው በአጋጣሚው ሊያታልል መፈለጉን ተረዳ። "ልጄ! ተወው ይቀበር።" ብሎ ቢለምነው "አይሆንም! ምን ታመጣለህ?" አለው።

ያን ጊዜ አባ መርትያኖስ ጸልዮ የሞተውን "በስመ እግዚአብሔር ተነስ።" ሲል አዘዘው። የሞተውም አፈፍ ብሎ ተነሳ። በዚህ ጊዜ ያ ሐሰተኛ በድንጋጤ ወድቆ ሞተ። ለዚህኛው በተዘጋጀው መቃብርም ላይ ቀበሩት። ከሞት የተነሳው ግን በደስታ ከወገኖቹ ጋር ሔደ። አባ መርትያኖስም ከዘመናት በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል።

አምላከ አበው ኃይለ ተአምሩን፣ ረድኤተ ምሕረቱን አያርቅብን። ከአባቶቻችን በረከትም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት፣ ቅዱስ አስከናፍር እና ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አእላፍ መላእክት <3

እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል።

መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ።
፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።)
፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ)
፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ)
፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል)
፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል)
፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል)
፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል)
፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል)
፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል)
፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው።

ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው።
አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው።
መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው።

መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው።

ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ።

ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ።
ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ።
(ዘካ. ፩፥፲፪)
ምሥጢርን ይገልጣሉ።
(ዳን. ፱፥፳፩)
ይረዳሉ።
(ኢያ. ፭፥፲፫)
እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ።
(መዝ. ፺፥፲፩)
ያድናሉ።
(መዝ. ፴፫፥፯)
ስግደት ይገባቸዋል።
(መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰)
በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ።
(ማቴ. ፳፭፥፴፩)
በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ።

ይህ ዕለት በሊቃውንት አንደበት "አእላፍ" እየተባለ ይጠራል። በሃይማኖት፣ በተልእኮትና በምስጋና የሚኖሩ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት በአንድ ላይ የሚከበሩበት ቀን ነው። ምንም እንኳን የጐንደሩን ፊት ሚካኤልን ጨምሮ በአንዳንድ አድባራት ታቦቱ ቢኖርም ሲያነግሡ ተመልክቼ አላውቅም።

ሊቃውንቱ በማኅሌት፣ ካህናቱም በቅዳሴ እንደሚያከብሯቸው ግን ይታወቃል። ኅዳር ፲፫ ቀን ዓመታዊ በዓላቸው ነው ማለት በየወሩ በአሥራ ሦስት ወርኀዊ በዓላቸው መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልናስባቸው ይገባል።

ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱሳን መላእክትን በስምና በማዕረግ እንደሚነግረን ሁሉ በማኅበር (በትዕይንት) አገልግሎታቸውም ይነግረናል። ለምሳሌ፦
ያዕቆብ በረዥም መሰላል ሲወጡና ሲወርዱ ተመልክቷል።
(ዘፍ. ፳፰፥፲፪)
ኤልሳዕ ለግያዝ አሳይቶታል።
(፪ነገ. ፮፥፲፯)
ዳንኤል ተመልክቷል።
(ዳን. ፯፥፲)
በልደት ጊዜ በዝማሬ መገለጣቸውን ቅዱስ ሉቃስ ጽፏል።
(ሉቃ. ፪፥፲፫)
ዮሐንስ በራዕዩ አይቷቸዋል።
(ራዕይ. ፭፥፲፩)

ከዚህም በላይ በብዙ የመጻሕፍት ክፍል ተጠቅሰዋል። ቅዱሳን መላእክተ ብርሃን፣ መንፈሳውያን፣ ሰባሕያን፣ መዘምራን፣ መተንብላን (አማላጆች) ተብለውም ይጠራሉና ያስቡን ዘንድ ልናስባቸው ይገባል።

<3 ቅዱስ አስከናፍር ሮማዊ <3

የዚህ ቅዱስ ሰው ሕይወት ታሪክ ደስ የሚያሰኝና የሚያስተምር ነው። ቅዱሱ የገዳም ሰው አይደለም። በሮም ከተማ እጅግ ሃብታም፣ ባለ ትዳር፣ የአንድ ልጅ አባትና የከተማዋ መስፍን ነው። ይህ ሰው በጣም ደግና አብርሃማዊ ነው።

ከጠዋት እስከ ማታ ነዳያንን ሲቀበልና ሲጋብዝ ነበር የሚውለው። ነገር ግን አንድና ብቸኛ ልጁ መጻጉዕ (ድውይ) ሆነበት። ለሠላሳ አምስት ዓመታትም ከአልጋ ላይ ተጣብቆ ይኖር ነበር። ቅዱስ አስከናፍር ግን ፈጣሪውን ያማርር ደግነቱን ይቀንስ ዘንድ አልሞከረም። አሁንም ነዳያኑን ማጥገቡን እንግዳ መቀበሉን ቀጠለ እንጂ።

በዚያ ወራት ደግሞ በሮም ግዛት ቋንጃ የሚቆርጡ ሰው እየገደሉ የሚዘርፉ አሥራ ሦስት ሽፍቶች ነበሩ። ስለ ቅዱስ አስከናፍር ደግነት ሰምተው ገድለው ይዘርፉት ዘንድ ተማከሩ። የሠራዊት አለቃ በመሆኑ በማታለል ሔዱ።

መነኮሳትን ይወዳልና አሥራ ሦስቱም ልብሰ መነኮሳትን ለብሰው ሰይፎቻቸውን ደብቀው ከበሩ ደርሰው "የእግዚአብሔር እንግዶች ነን፤ አሳድረን?" አሉት። ቅዱስ አስከናፍር ድምጻቸውን ሲሰማ ደነገጠ።

ብቅ ብሎ አያቸውና "ጌታዬ! ምንም ኃጢአተኛ ብሆን አንድ ቀን ወደ ባሪያህ እንደምትመጣ አምን ነበር።" ሲል በደስታ ተናገረ። እንዲህ ያለው ሽፍቶቹ አሥራ ሦስት በመሆናቸው ጌታ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት አስከትሎ የመጣ መስሎት ነው።

ወዲያውም ወደ ቤቱ አስገብቶ እግራቸውን አጠባቸው። የእግራቸውን እጣቢ ወስዶም በልጁ ላይ አፈሰሰበት። ድንገትም ለሠላሳ አምስት ዓመታት አልጋ ላይ ተጣብቆ የኖረው ልጅ አፈፍ ብሎ ከአልጋው ላይ ተነሳ።
በዚህ ጊዜ ቅዱስ አስከናፍር ለአሥራ ሦስቱ ሽፍቶች በግንባሩ ሰገደ። ሽፍቶቹ ግን ነገሩ ግራ ቢገባቸው ደነገጡ።

ጌታ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት አስከትሎ መምጣቱን የሰሙ የሃገሩ ሰዎችም እየመጡ ይሰግዱላቸው ገቡ። በዚህ ጊዜ ሽፍቶቹ ልብሳቸውን አውልቀው እውነቱን ተናገሩ። "እኛ ሽፍቶች ነን። የመጣነውም ልንገልህ ነው። አምላክ ግን ባንተ ደግነት ይህንን ሁሉ ሠራ። አሁንም እባክህ ትገድለን ዘንድ ሰይፋችንን ውሰድ።" አሉት።

እርሱ ግን "ንስሐ ግቡ እንጂ መሞት የለባችሁም።" ብሎ ስንቅ ሰጥቶ አሰናበታቸው። አሥራ ሦስቱ ሽፍቶችም ጥቂት ምስር ይዘው ወደ ተራራ ወጡ። ምስሩን በመሬት ላይ በትነው ማታ ብቻ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት ተጋደሉ። በዚህች ቀን አሥራ ሦስቱም በሰማዕትነት የክብር አክሊልን ተቀዳጁ። ቅዱስ አስከናፍርም በተቀደሰ ሕይወቱ ተግቶ ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት <3

ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር። ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል።

ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል ክብርና ርኅሩኅ የለም። በምልጃውም፣ በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው። መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል። "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል። ቂም የሌለው ለምሕረት የሚፋጠን ደግ መልአክ ነውና።

በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ፣ ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል። እስራኤልን አርባ ዘመን በበርሃ መርቷል፤ መግቧልም። ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል።
(ዘፍ. ፵፰፥፲፮ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ መሳ. ፲፫፥፲፯ ፣ ዳን. ፲፥፳፩ ፤ ፲፪፥፩ ፣ መዝ. ፴፫፥፯ ፣ ራዕይ. ፲፪፥፯)

ደስ የሚለው ደግሞ ርኅሩኁ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው። ከእናቷ ማኅጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ። ደስ ብሎት ይታዘዛታል። ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ።" ይላታል። ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን፣ በረከትን ያወርዳሉ።

<3 ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ <3

ዳግመኛ በዚህች ዕለት ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን እንደ ረዳው ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምራለች። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ ፭ ላይ እንደ ተጻፈው ቅዱሱ መልአክ ለኢያሱ ተገልጦለታል። እስራኤልን በምድረ በዳ የመራ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ሲያርፍ ታላቅ ሐዘንና ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር።

እግዚአብሔር ግን ኢያሱን አስነስቶ አረጋግቷቸዋል። ቅዱስ ሚካኤል አርባውን ዘመን እስራኤልን ደመና ጋርዶ፣ መና አውርዶ፣ ክንፉን ዘርግቶ፣ ጠላትን መክቶ ከሙሴ ጋር እንደ መራቸው ከኢያሱ ጋርም ይሆን ዘንድ ከሰማይ ወረደ።

በኢያሪኮ አካባቢም የተመዘዘ ሰይፉን ይዞ በግርማ ለኢያሱ ታየው። ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ "አንተ ከእኛ ወገን ነህን? ወይስ ከጠላቶቻችን?" ሲል ጠየቀው። ቅዱስ ሚካኤልም መልሶ "እረዳህ ዘንድ እነሆ የሠራዊት አለቃ ሆኜ ተሹሜ መጥቻለሁ።" አለው።

ያን ጊዜ ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ በግንባሩ ተደፍቶ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰገደለት። ቅዱሱ መልአክም አክሎ "ፍታሕ ቶታነ አሳዕኒከ እም እገሪከ እስመ ምድር እንተ ትከይዳ ቅድስት ይዕቲ - የረገጥካት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ።" አለው።

ኢያሱም የተባለውን አደረገ። ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን "ለመላእክት የጸጋ (የአክብሮ) ስግደት ይገባል፤ በቅዱሳኑ ፊትም ጫማ ተለብሶ አይቆምም።" የምትለው። ያ መሬት ሊቀ መላእክት ቢቆምበት ተቀድሷል። ዛሬም ቤቱ በታነጸበት ታቦቱ በተቀረጸበት ቦታ ሁሉ ቅዱሱ መልአክ አለና ጫማን አውልቆ ባጭሩ ታጥቆ መግባት ይገባል።

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከኢያሱ ጋር ሆኖ አማሌቅን ጨምሮ የእስራኤልን ጠላት አጥፍቷል። ጥቅመ ኢያሪኮን (ቅጥሩን) አፍርሷል። ምድረ ርስትን አውርሷል። በገባኦን ፀሐይን፣ በቆላተ ኤሎምም ጨረቃን ሲያቆም ከእርሱ ጋር ሆኖ ረድቶታል።

<3 ዱራታኦስና ቴዎብስታ <3

ቅዱሳኑ ዱራታኦስ (ዶርታኦስ) እና ቴዎብስታ (ቴዎብስትያ) የቅዱስ ሚካኤል ወዳጆች ናቸውና በዚህች ዕለት ይታሰባሉ። በድርሳነ ሚካኤልና በመጽሐፈ ስንክሳር ተጽፎ እንደምናገኘው ሁለቱ ቅዱሳን በተቀደሰ ትዳር ተወስነው፣ ሕጉን ትዕዛዙን ፈጽመው፣ ለነዳያን ራርተው፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው የሚኖሩ ነበሩ።

ይልቁኑ ግን የጌታችንን፣ የእመቤታችንን እና የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ያለማስታጐል ያደርጉ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሃብት ንብረታቸው አልቆ ተቸገሩ። ግን የጨነቃቸው መቸገራቸው ሳይሆን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ሊያቆሙ መሆናቸው ነው።

አማራጭ ሲያጡ ተቀምጠው ተመካከሩ። የቅዱሱ መልአክ ዝክር ከሚቀር ልብሳቸውን (ያውም የክብር ልብሳቸውን) ሊሸጡ ተስማሙ። በዚህ መሰረት ቅዱስ ዱራታኦስ ወደ ገበያ ሲሔድ ወዳጁ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወረደለት።

መንገድ ላይም የጦር መኮንን ሃገረ ገዢ መስሎ ተገናኝቶ አጫወተው። ችግሩን ጠይቆም መፍትሔውን ነገረው። "እኔ እዋስሃለሁና ለበዓል የሚያስፈልጉህን ነገሮች ሁሉ ገዝተህ አሰናዳ።" አለው።

"እኔ ወደ ቤትህ መጥቼ ስለምስተናገድ አንድ ዓሣ አምጥተህ አቆየኝ። እኔ ሳልመጣ ግን አትረደው።" አለው። ቅዱስ ዱራታኦስ የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ ወደ ቤቱ ሲሔድ ድንቅ ነገርን ተመለከተ። ሚስቱ ቅድስት ቴዎብስታ በቤቱ መካከል ሁና ቤቱ በበረከት ሞልቷል።

ማሩ፣ ቅቤው፣ እሕሉ ሁሉ በየሥፍራው ሞልቷል። ባልና ሚስቱ ደስ ብሏቸው። ነዳያንን ሲያበሉ እንግዳ ሲቀበሉ ዋሉ። በኋላ ያ መኮንን (ቅዱስ ሚካኤል) በቤታቸው መጥቶ ተስተናገደ።

በእርሱ ትዕዛዝ የዓሣው ራስ (ሆድ) ሲከፈት በውስጡ ሦስት መቶ ዲናር ወርቅ (እንቁ) ተገኘ። ቅዱሳኑ ይህን ተመልክተው ሲደነግጡ ቅዱስ ሚካኤል ክንፉን ዘርግቶ ራሱን ገለጸላቸው። ደንግጠው በግንባራቸው ተደፉ።

እርሱ ግን "በተገኘው ሃብት እዳችሁን ክፈሉ። ከዚህ በኋላ ግን በምድር አትቸገሩም። በሰማይም ክፍላችሁ ከእኔ ጋር ነው።" ብሎ ባርኳቸው ወደ ሰማይ ዐረገ። እነርሱም በሐሴትና በበጐ ምግባር ኖረው ዐርፈዋል። ለርስቱም በቅተዋል።

<3 ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ <3

የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ፣
በሕፃንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ፣
በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ፣
በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ፣
ምጽዋትን ያዘወተረ፣
አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው።
ዐርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል።

<3 አፄ በእደ ማርያም <3

"በዕደ ማርያም" ማለት "በማርያም እጅ" እንደ ማለት ነው። እኒህ ሰው የኢትዮጵያ ንጉሥ ሲሆኑ የነገሡትም በ፲፬፻፷ ዓ/ም ነው። ደጉ አባታቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሲያርፉ በመንግስቱ ተተክተው ሃገራችንን አስተዳድረዋል። ድርሰት ደርሰዋል። አብያተ መቃድስ አንጸዋል።

በተለይ ለቅኔ ትምህርት ማበብ ልዩ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገራል። ልክ በነገሡ በአሥር ዓመታቸው ግን መንግሥተ ምድር በቃኝ ብለው በምናኔ በርሃ ገብተዋል። በዙፋናቸውም አፄ እስክንድር ተተክተዋል። ጻድቁ ንጉሥ ግን ቅዱስ ሚካኤልን ይወዱት ነበርና በዚህች ቀን ዐርፈዋል።

አምላከ ቅዱሳን በክንፈ ሚካኤል ከክፉው ሁሉ ይሰውረን። ከበረከታቸውም አይለየን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅድስት ወብጽዕት ሐና (እመ ማርያም) ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ብጽዕት ሐና <3

"ሐና" ማለት በዕብራይስጥኛው "የእግዚአብሔር ስጦታ" እንደ ማለት ነው። "ሐና፣ ዮሐና፣ ሐናንያ" የሚሉ የዕብራይስጥ ስሞች ትርጉማቸው ተወራራሽ ነው። የዚህችን ቅድስት እናት ክብሯን መናገር የሚችል የለም። እርሷ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ወልድ በሥጋ አያቱ ተብላለችና።

አንድም ለሰማይና ለምድር ንግሥት ለድንግል ማርያም ወላጅ እናቷ ናትና። ከዓለም ሴቶች ሁሉ የቅድስት ሐና ማኅጸን እንደ ምን ይከብር! በፍጥረት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥንተ አብሶ (የአዳም በደል) መተላለፍ የቀረው በማኅጸነ ሐና ውስጥ ነውና። (ለዚህ አንክሮ ይገባል!)

ይስሐቅን የተሸከመ የሣራ ማኅጸን ቡሩክ ከተባለ የቅድስት ሐናማ እንደምን አይባል! ከፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ድንግል ማርያምን እንደ መረጠ ሁሉ ቅድስት ሐናንም ለአያትነት መርጧታል።

ቅድስት ሐና ትውልዷ፣ ነገዷ ከላይ ከቅዱስ አብርሃም፣ ከታች ደግሞ ከነገደ ካህናት ነው።
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅ ያዕቆብን፣ ያዕቆብ ደግሞ ሌዊንና አሥራ አንድ ወንድሞቹን ይወልዳል።
ሌዊ ቀዓትን፣ ቀዓት እንበረምን፣ እንበረም አሮን ካህኑን ይወልዳሉ።
ቅዱስ አሮን አልዓዛርን፣ አልዓዛር ፊንሐስን እያለ ትውልዱ እስከ ቴክታና በጥሪቃ ይወርዳል። ቴክታና በጥሪቃም ልጅ በማጣት ኖረው የእንቦሳዎች፣ የፀሐይና የጨረቃን ምሥጢር ተመልክተው ሄኤሜንን ይወልዳሉ።
ሄኤሜን ዴርዴን፣ ዴርዴ ቶናሕን፣ ቶናሕ ሲካርን፣ ሲካርም ሔርሜላን ይወልዳሉ።
ሔርሜላም ከክርስቶስ ልደት ዘጠና ዓመታት በፊት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) የሚባል ደግ ሰው ከካህናት ወገን አግብታ በስርዓተ ኦሪት ትኖር ነበር። እግዚአብሔር ለዚህች ደግ ሴት የተባረኩ ሦስት ሴቶች ልጆችን ሰጣት።

የመጀመሪያዋን "ማርያም" አለቻት። ይህቺውም የአረጋዊው ዮሴፍ ሚስትና የቅድስት ሰሎሜ ቡርክት እናት ናት። ሁለተኛዋን "ሶፍያ" አለቻት። እርሷም ቅድስት ኤልሳቤጥን (የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን እናት) ወልዳለች።

በመጨረሻ የወለዷትን ግን "ሐና" አሏት። ይህቺውም የፈጣሪ የሥጋ አያቱ፣ የድንግል ማርያምም እናቷ ትሆን ዘንድ የተመረጠችውና ስም አጠራሯ የከበረው ዛሬ የምናከብራት እናት ናት።

መጽሐፈ ስንክሳርን ስመለከት እንዲህ የሚል ዓረፍተ ነገር አየሁ። "ለዛቲ ቅድስት ኢያዕመርነ ገድላቲሃ ዘትገብሮን በኅቡዕ ከመ ንዝክሮን" ይላል። ትርጉሙም "የዚህችን ቅድስት ገድሏንና ትሩፋቷን እንዳንዘረዝር አላወቅነውም።" እንደ ማለት ነው።

የሚገርመው አበው እንዲህ ያሉት ክብሯን መግለጹን አልጠግብ ብለው ነው። እኛም በመጠናችን የብጽዕት ሐናን ሕይወት በአጭሩ ቀጥለን እንመልከት።

ብጽዕት ሐና ወላጆቿ (ማጣትና ሔርሜላ) ከካህናት ወገን በመሆናቸው ልጆቻቸውን በጥንቃቄ በሥርዓተ ኦሪት እንዳሳደጉ ይታመናል። ቅድስት ሐናንም ለአቅመ ሔዋን እስክትደርስ ድረስ በሕጉ፣ በሥርዓቱ አሳድገዋታል።

በወቅቱ በፈቃደ እግዚአብሔር ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ የሚሆን አንድ ደግ ሰው አጩላት። ይህ ሰው "ኢያቄም" ይባላል። አንዳንዴም "ሳዶቅ" ወይም "ዮናኪር" እየተባለ ይጠራል። ቅዱስ ኢያቄም ማለት ክፉ ከአንደበቱ የማይወጣው፣ ምጽዋትን የሚወድ፣ አምላከ እስራኤልን በንጹሕ ልቡ የሚያመልክ ሰው ነበረ።

እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ሁለቱ (ኢያቄም ወሐና) ከተጋቡ በኋላ ቶሎ መውለድ አልቻሉም። ይህ ደግሞ የወቅቱ ከባድ ፈተና ነው። በዘመድ የከበሩ፣ በጠባያቸው የተመሰገኑ፣ መልካምንም የሚሠሩ ሰዎች ልጅ ስለሌላቸው ብቻ "ኅጡአነ በረከት" እየተባሉ ከቤተ እግዚአብሔር ይገፉ፣ በአደባባይም ይነቀፉ ነበር።

ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ልጅ አለመውለድ እንደ ኃጢአተኛ ያስቆጥር ነበር። ደግነቱ የወቅቱ ሊቀ ካህናት ቅዱስ ዘካርያስ (የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አባት) እንደ እነሱ ልጅ ያጣ በመሆኑ አብረው ይጽናኑ ነበር።

የሆነው ሆኖ እኒህ ቡሩካን ሰዎች አምላከ እስራኤልን ከመለመንና ከማመስገን በቀር ሌላ ትርፍ አልተገኘባቸውም። ምንም የሞላቸውና የደላቸው ባይሆኑም ደሃን ሳያጐርሱ አይበሉም ነበር።

ቅድስት ሐናን ግን "ቢወልዷት እንጂ አትወልድ።" እያሉ ጐረቤቶቿ ይሳለቁባት ነበር። ከማልቀስ በቀር ደግሞ መልስ አልነበራትም።

አንድ ቀን ግን ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ ተመልክታ "ፈጣሪ ሆይ! የእንስሳትን ማኅጸን የምትከፍት ዕፅዋትንም ከባሕርያቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ:: እውነትም ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ስትል አለቀሰች።

ቅዱስ ኢያቄምም ወደ ተራራ ወጥቶ ለአርባ ቀናት አለቀሰ፤ ተማለለ። ይህ ሲሆን ሁለቱም አርጅተው ነበር። ሐምሌ ሠላሳ ቀን ግን ነጭ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ በማኅጸነ ሐና ስታድር አዩ። ደስ ብሏቸው ለሰባት ቀናት ሱባኤ ይዘው ቅድስት ሐና እመቤታችንን ነሐሴ ሰባት ቀን ጸነሰቻት።

ይህም ለእነርሱም ለወገኖቻቸውም ታላቅ ተድላ ሆነ። ብጽዕት ሐና ግን ፈጣሪዋን ታከብረው ዘንድ በጐነትንና ንጽሕናን አበዛች። ጸንሳ ሳለም ዕውራንን አበራች፤ ድውያንን ፈወሰች።

የጦሊቅ ልጅ በሞተ ጊዜም እያለቀሰች ስትዞረው ጥላዋ ቢያርፍበት አፈፍ ብሎ ተነስቶ፦ "ሰላም ለኪ እሙ ለፀሐየ ጽድቅ" ብሎ ድንግል ማርያምን "ወሰላም ለኪ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ" ብሎ ቅድስት ሐናን አመስግኗል። ትርጉሙም ድንግልን "የፀሐየ ጽድቅ እናቱ" ሐናን "ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አያቱ" ማለት ነው።

ይህንን ያዩ አይሁድ ቅድስት ሐናን ሊገድሉ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ግን መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አልፈቀደላቸውም። ግንቦት ፩ ቀንም የሰማይና የምድር ንግሥትን ሊባኖስ ተራራ ላይ ወልዳ ሽሙጥን ከሁላችንም አራቀች።

ስሟን "ማርያም - የአምላክ ስጦታ" ብለው ሰይመው ለሦስት ዓመታት አሳድገዋታል። የሚገርመው በሦስቱ ዓመታት ውስጥ ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከክንዷ አውርዳት አታውቅም ነበር። አንድ ጊዜም መላእክት ወስደውባት ፍጹም አልቅሳለች። ኋላ ግን መልሰውላታል።

ሌላኛው የሚደንቀው እግዚአብሔር የዓለም ውዱን ስጦታ እመ ብርሃንን ሰጣቸው። እነርሱም ይህችን ውድ ስጦታ ሳይሰስቱ ለፈጣሪ መለሱለት።
"እምቅድሜክሙ አልቦ
ወእምድኅሬክሙ አልቦ
ከመዝ መስዋዕት ለእግዚአብሔር ዘወሃቦ።" እንዲል።

ቅድስት ሐና ድንግል ወደ ቤተ መቅደስ ከገባች በኋላ የእናትነት ፍቅሯ እያገበራት ለአምስት ዓመታት እየተመላለሰች ትጐበኛት፤ ትስማት ነበር። እመቤታችን ስምንት ዓመት በሞላት ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ቅድስት ሐና ደረሰ።

ከክርስቶስ ልደት ስምንት ዓመታት አስቀድማ ብጽዕት እናት ሐና በዚህች ቀን ዐረፈች። ትንሽ ቆይቶም ባለቤቷ ቅዱስ ኢያቄም ተከተላት እኛም ልጆቿ "ብጽዕት ሐና ብጽዓን ይገባሻል!" እያልን እናመስግናት።

ሊቃውንቱ ለእርሷ እንዲህ ብለዋልና፦
"ሰላም ለኪ ለጸሎተ ኩሉ ምዕራጋ
ከመ አስካለ ወይን ዲበ ሐረጋ
ሐና ብጽዕት ተፈስሒ እንበለ ንትጋ
እስመ ረከብኪ ሞገሰ ወአድማዕኪ ጸጋ
እምሔውተ አምላክ ትኩኒ በሥጋ።" (አርኬ)

አምላከ ብጽዕት ሐና በምልጃዋ ከዘላለም እሳት ያድነን። ጸጋ በረከቷንም ይክፈለን።

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅዱሳን ታቦትና ኖኅ (ወላጆቹ)
፫.ቅዱስ ሮማኖስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.ቅዱስ አቡፋና ጻድቅ
፮.ታላቁ አባ ቢጻርዮን

"የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ። ተፈተኑ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ፣ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ፣ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና።"
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ሃያ አራቱ ቅዱሳን ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል)
፪.ቅዱስ አዝቂር ሰማዕት
፫.ቅዱስ ኪርያቅ ሰማዕት
፬.አርባ ስምንት ሰማዕታት (ማኅበሩ)
፭.አባ ዮሴፍ ዘሃገረ ጻን
፮.ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጥዑመ ዜና

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምህረ ትሩፋት)
፪.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፫.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
፬.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤጲስቆጶስ)
፭.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮጵያዊ)
፯.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

"በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ። በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር። ከዙፋኑም መብረቅና ድምጽ ነጐድጓድም ይወጣል። በዙፋኑም ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ ነበር። እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።"
(ራእይ ፬፥፬-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

"ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! አንተን በመታመን ለጠራህ ሁሉ ፈጥነህ ስትደርስለት ከዓውሎ ነፋስ ይልቅ በተፋጠነ ሩጫ ነው እኮን።
ጊዮርጊስ ሆይ! የዘወትር ጸሎቴንና የቃሌንም የልመና ጩኸት ትቀበል ዘንድ ለይቅርታና ለምሕረት ፈጥነህ ወደ እኔ ቅረብ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን ቆዝሞስ ወድምያኖስ (ሰማዕታት)
፪.ቅድስት ቴዎዳዳ (እናታቸው)
፫.ቅዱሳን አንቲቆስ፣ ዮንዲኖስና አብራንዮስ (ወንድሞቻቸው)
፬.ሦስት መቶ አሥራ አንድ ሰማዕታት (የነ ቆዝሞስ ማኅበር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፫.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
፬.አባ ጳውሊ የዋህ
፭.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
፮.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ሐዋርያ

"ልጆች ሆይ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ አሸንፋችኋቸውማል። በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። እነርሱ ከዓለም ናቸው። ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ። ዓለሙም ይሰማቸዋል። እኛ ከእግዚአብሔር ነን። እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል። ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም።"
(፩ዮሐ ፬፥፬-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘሮም <3

በቤተ ክርስቲያን እጅግ ስመ ጥር ከሆኑት ሊቃውንት አንዱ ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚታወቀው "ገባሬ መንክራት" በሚለው ስሙ ነው። ገባሬ መንክራት የተባለውም እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን በመሥራቱ ነው።

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ሥር ተወልዶ ያደገው ቅዱስ ጐርጐርዮስ ከመመነኑ በፊት ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል። እርሱ በበርሃ እያለም ከሮም ጳጳሳት የአንዱ በማረፉ ተሿሚ ፍለጋ አበው ሱባኤ ገቡ። እግዚአብሔርም "የበረሃውን ጐርጐርዮስን ፈልጉት።" አላቸው።

"እሺ!" ብለው ፍለጋ በርሃ ቢሔዱ ውዳሴ ከንቱን ይጠላልና ተሰወረባቸው። እነርሱም እያዘኑ ተመልሰው በመንበረ ጵጵስናው ላይ ወንጌልን አኖሩና ተለያዩ። በዚህ ጊዜ ቅዱስ መልአክ ወርዶ "ጐርጐርዮስ ሆይ! ልትሔድ ይገባሃል።" አለው።

እርሱም ወደ ከተማ ወርዶ ታላቁ ሊቅ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ባለበት በዓለ ሲመቱ ተከብሯል። ቅዱስ ጐርጐርዮስ በዘመኑ ብዙ መጻሕፍትን ደርሶ፣ የክርስቶስን መንጋም ጠብቆ፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትንም ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል።

ከተአምራቱም፦
ወንድማማቾች ከአባታቸው በወረሷት አንዲት ሐይቅ እየተጣሉ ሲያስቸግሩ በጸሎቱ ሐይቁን የብስ አድርጐ አስታርቋቸዋል።

<3 ቅዱስ ዮሐንስ ዘአስዩጥ <3

በአራተኛውና በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመናት ከተነሱ ከዋክብት ጻድቃን አንዱ ነው። እድሜው በጣም ረዥም በመሆኑ የብዙ ቅዱሳን ባልንጀራም ነበር። በገድል አካሉን ቀጥቅጦ በስብከትም የአስዩጥን (አሲዩትን) ምዕመናን አንጾ ብዙ ተአምራትን ሠርቶ በተወለደ በመቶ ሃያ አምስት ዓመቱ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል።

አምላከ ቅዱሳን የአማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያምን ጣዕሟን፣ ፍቅሯን፣ ጸጋ በረከቷን ያሳድርብን። ከአበው በረከትም አይለየን።

ኅዳር ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ጽዮን ድንግል ማርያም
፪.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘሮሜ
፫.ቅዱስ ዮሐንስ ዘአስዩጥ
፬.ቅዱስ ቆዝሞስ ሊቀ ጳጳሳት
፭.ቅድስት ዲቦራ ዘድልበት
፮.ቅዱስ ዘኬዎስ ሐጺር

ወርኀዊ በዓላት
፩.አበው ጎርጎርዮሳት
፪.አቡነ ምዕመነ ድንግል
፫.አቡነ አምደ ሥላሴ
፬.አባ አሮን ሶርያዊ
፭.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

"ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል። እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ።.....
የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ። የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ። የእግዚአብሔርም ከተማ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።"
(ኢሳ ፷፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለኃያል ሰማዕት ማር ቴዎድሮስ እና ቅዱስ አንያኖስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ቴዎድሮስ ማር ሰማዕት <3

በቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ የሆነው ማር ቴዎድሮስ የተወለደው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። አባቱ ዮሐንስ በትውልድ ግብጻዊ የሆነ ክርስቲያን ነው። እናቱ ግን አስቸጋሪና ጣዖት አምላኪ ሶርያዊት ነበረች።

ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስት ባሏ ክርስቲያን መሆኑን አታውቅም ነበር። ቴዎድሮስ (የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው።) በተወለደ ጊዜ ግን ጠብ ተነሳ። እሱ ክርስትና ለማስነሳት ሚስት ደግሞ ወደ ጣዖት ቤት ለመውሰድ ተጋጩ። ሚስት ወገኖቿ ባለሥልጣኖች ናቸውና ልጁን ቀምታ ባሏን ዮሐንስን ወደ ግብጽ አሳደደችው።

ዮሐንስ በስደት ባለበት ሃገር ስለ ልጁ ፈጽሞ ይጸልይ፣ ያለቅስም ገባ። እግዚአብሔር ደግሞ ልመናውን ሰማ። ማር ቴዎድሮስ ወጣት በሆነ ጊዜ ማንም ሳይጠራው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተማረ፤ ተጠመቀ። ዕለት ዕለትም ጾምና ጸሎትን ከምጽዋት ጋር ያበዛ ድንግልናውን ለመጠበቅ ይተጋ ነበር።

በዛው ልክ ደግሞ ገና በሃያ ዓመቱ በጉልበቱ ኃያል፣ በውበቱም ደመ ግቡ፣ በጠባዩም ገራገር ነበርና ተወዳጅ ነበር። ነገሥታቱም የአንጾኪያ የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ሾሙት። እነሆ እስከ ዛሬ "የሠራዊት አለቃ" ተብሎ ይጠራል።

ማር ቴዎድሮስ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም። ይልቁኑ የነገሥታቱን (የጠላት) ልጆች በመማረክ ነው የሚታወቀው። እንዲያውም አንድ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በተደረገ ጦርነት ብቻውን አሸንፏቸዋል።

የፋርስ ሰዎች ሊዋጉ ሲመጡ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ሰይፍ ሰጠው። ፋርሶችን "በከንቱ ከምትጠፉ ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ።" አላቸው። እነርሱ ግን ተሳለቁበት። ከፈረሱ ወርዶ ወደ ምስራቅ ዙሮ ጸልዮ በመስቀል አማተበ። በመካከላቸው ገብቶም በመልአኩ ሰይፍ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር አጠፋቸው።

አንድ ቀን ወደ አንድ ከተማ ቢገባ ዘንዶ ሲመለክ አገኘ። ይባስ ብሎ የአንዲት ክርስቲያን ልጆችን ለመስዋዕትነት ሲያቀርቧቸው ተመለከተ። በስመ ሥላሴ አማትቦ በፈረሱ ላይ ተቀምጦ ዘንዶውን በጦር ገደለው። የዘንዶውም ርዝመት ሃያ አራት ክንድ ነበር።

ከነገር ሁሉ በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ስለ አባቱ ወሬ ሰምቶ ካለበት ሥፍራ አፈላልጎ አግኝቶ ደስ አሰኘው። እስኪያርፍ አብሮት ቆይቶ ቀብሮት ወደ አንጾኪያ ሲመለስ ግን የሚያሳዝን ነገር ጠበቀው።

ክርስቶስ ተክዶ፣ ጣዖት ቁሞ፣ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው፣ የክርስቲያኖች ደም ፈሶ፣ ከተማዋ በግፍ ተሞልታ ተመለከተ። እርሱም በዚያች ሰዓት መወሰን ነበረበትና አደረገው። የሁሉ ሠራዊት አለቃ ቢሆንም የክብር ልብሱን አውልቆ ባጭር ታጥቆ በንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ፊት ቆመ።

ማር ቴዎድሮስ በአደባባይ እንዲህ ተናገረ፦ "አንሰ አመልኮ ለክርስቶስ ንጉሠ ስብሐት በኩሉ ልብየ ወእሠውዕ ሎቱ - እኔስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን በፍጹም ልቤ አመልከዋለሁ፤ ለእርሱም ብቻ እሠዋለሁ።" ንጉሡ በቁጣ መሬት ላይ ጥለው እንዲደበድቡት አዘዘ። ወታደሮቹ ደሙ እስኪንጠፈጠፍ ገረፉት።

በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃይተው በእሳት አቃጠሉት። እርሱ ግን በጸሎቱ እሳቱን ውኃ አደረገው። ወታደሮቹ እርሱን በብዙ አሰቃዩት። እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ጸና፤ ታገሠ።

በመጨረሻም ጌታችን በግርማ ወርዶ "ወዳጄ ቴዎድሮስ ስምህን የጠራ፣ መታሠቢያህን ያደረገ፣ ገድልህን (ዜናህን) የጻፈ፣ ያጻፈ፣ ያነበበ፣ ገዝቶ በቤቱ ውስጥ ያኖረውን ሁሉ እምርልሃለሁ።" አለው።

በስሙም ረድኤት እንደሚደረግ ነግሮት ዐረገ። ወታደሮቹም በዚህ ቀን አንገቱን ሰይፈው የክብር አክሊልን ተቀብሏል። እጅግ ብዙ ሺህ ሰዎችም አብረውት ተሰይፈዋል።

<3 ቅዱስ አንያኖስ ዘግብጽ <3

ይህ ቅዱስ አባት ውለታው ከፍ ያለ ነውና በምድረ ግብጽ እጅግ ይከበራል። በተለይ ክርስትናን ከሐዋርያት ተቀብሎ ለምዕመናን ያስረከበ አባት በመሆኑ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ወንጌላዊው ሐዋርያ ቅዱስ ማርቆስ በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ተመድቦ በፈቃደ እግዚአብሔር ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ በ፶ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ወደ ምድረ ግብጽ ወረደ።

እስክንድርያ ከተማ በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ እንደ መኖሯም መጀመሪያ ወደ እርሷ ደረሰ። ልክ ወደ ከተማ ሲገባ ገና አንደበቱ ለወንጌል ሳይከፈት እንቅፋት መትቶት ጫማው ተበጠሰ። ያን ሁሉ በርሃ የቻለች ጫማ በእንቅፋት በመበጠሷ እያዘነ ወደ ጫማ ሰፊ ዘንድ ደርሶ "ሥራልኝ?" ይለዋል።

ይህ ጫማ ሰፊ አንያኖስ (አንያኑ) ይባላል። ጣዖት አምላኪ ግን ደግሞ ቅንና ገር የሆነ ሰው ነበር። "እሺ" ብሎ ሲሰፋለት መስፊያው ስቶ መሐል እጣቱን ስለ ወጋው "ኢታስታኦስ (አታኦስ)" ብሎ ጮኸ። ትርጉሙም "አንድ አምላክ" ማለት ነበር።

ይህንን የሰማው ቅዱስ ማርቆስ ቀና ብሎ "ጌታዬ ሆይ! ጐዳናዬን ስላቀናህልኝ አመሰግንሃለሁ!" ብሎ ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ የአንያኖስን እጅ ቀባው።

ወዲያውም ደሙ ቁሞ፣ ቁስሉም ድኖ እንደ ነበረው ሆነ። በዚህ ተአምር ድንጋጤም ደስታም ቢሰማው "ማነህ አንተ?" ሲል ቅዱሱን ጠየቀው። ወንጌላዊውም መልሶ "እኔ የክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ።" አለው።

አንያኖስም "እባክህ ወደ ቤቴ እንሒድ።" ብሎ ሐዋርያውን ጋበዘው። እቤት ሲደርሱም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር አስተናግደውት የሕይወትን ቃል ለመኑት። ቅዱስ ማርቆስም ከሥነ ፍጥረት እስከ ጌታችን የማዳን ሥራ አስተምሯቸው አመኑ። አጥምቆ ሥጋውን ደሙን አቀበላቸው።

ይህቺው የቅዱስ አንያኖስ ቤትም በምድረ ግብጽ የመጀመሪያዋ ጉባኤ ቤትና ቤተ ክርስቲያን ሆነች። ቅዱሱ ሐዋርያ በ፷ ዓ/ም አካባቢ በቅዱስ አንያኑ ቤት ሆኖ በርካቶችን አሳመነ። በሰማዕትነት ከማረፉ በፊትም ቅዱስ አንያኖስን የምድረ ግብጽ ሁሉ ሊቀ ጳጳሳት (ፓትርያርክ) አድርጐ ሾመው።

ቅዱስ አንያኖስም ለአሥራ ሁለት ዓመታት የክርስቶስን መንጋ እያበዛ ተጋደለ። ከሐዋርያው የተቀበለውን ንጹሕ ዘር ዘራ። የድኅነት የምስራቹንም አዳረሰ። ይሔው ይህ መልካም ተክል ዛሬም ድረስ ሳይጠወልግ አለ።

የአሁኑ ፓትርያርክ አቡነ ታውድሮስም ከቅዱስ ማርቆስ መቶ አሥራ ስምንተኛ ሲሆኑ ከቅዱስ አንያኖስ መቶ አሥራ ሰባተኛ ናቸው። ቅዱሱ ለእኛ ኢትዮጵያውያንም የክህነት አባታችን ነው። ይህች ቀንም ዕለተ ዕረፍቱ ናት።

አምላከ ቅዱሳን ክፉውን አርቆ ከበጐው ዘመን ያድርሰን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ማር ቴዎድሮስ ኃያል ሰማዕት
፪.ቅዱስ አንያኖስ (አንያኑ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፪.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፫.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፬.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፭.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

"በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ፤ አትናወጡም። ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት።"
(፩ጴጥ ፫፥፲፫-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ደናግል አጥራስስ ወዮና <3

እሊህ ቡሩካት ሴት ወጣቶችም ምድራቸው ሮም ናት። ቅድስት አጥራስስ የንጉሥ ልጅ ስትሆን ቅድስት ዮና ደግሞ የታላላቆች ልጅ ናት። ሁለቱ ቅዱሳት አንስት አይተዋወቁም ነበር። ዮና ገና በልጅነቷ ክርስትናን አጥንታለች።

አጥራስስ ግን አባቷ ጣዖት አምላኪ በመሆኑ ቤት ሠርቶ በወርቅ አንቆጥቁጦ ጣዖቶችን እንድታመልክ ሰውም እንዳታይ አደረጋት። እርሷ ግን ጣዖቱ እንደ ማይረባ ተመራምራ አውቃ ጣለችው።

"የማላውቅህ እውነተኛው አምላክ ተገለጽልኝ?" ስትልም ጸለየች። ያን ጊዜ ቅዱስ መልአክ "ዮና የምትባል ሴት ታስተምርሽ።" ስላላት አስፈልጋ አስመጣቻት። ቅድስት ዮናም ክርስትናን ከጥንቱ ጀምራ አስተማረቻት።

ሁለቱ ቅዱሳት አብረው እየዋሉ አብረው እያደሩ በጾምና በጸሎት ቢጠመዱ ድንግል ማርያም እመቤታችን ተገለጠችላቸው። ከልጇ ዘንድ አቅርባም አስባረከቻቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን የቅድስት አጥራስስ አባት ንጉሡ በሃገር አልነበረም። ሲመለስ ግን የሆነውን ሁሉ አወቀ።

ሕዝቡን ሰብስቦ በአንዲት ልጁ አጥራስስና በወዳጇ ዮና ላይ በእሳት እንዲሞቱ ፈረደባቸው። እሳቱ ብዙ እጥፍ ነዶ ሕዝቡ ሲያለቅስላቸው ሁለቱ ደናግል እርስ በርስ ተቃቅፈው ተሳሳሙ። እየጸለዩም ወደ እሳቱ ተወረወሩ። በዚያም ለፈጣሪያቸው ነፍሳቸውን ሰጡ። እሳቱ ግን ልብሳቸውን እንኳ አልነካውም።

አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ ሲል ቸርነቱን፣ ምሕረቱን ይላክልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ (ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት)
፪.ቅዱስ ኤላውትሮስና እናቱ እንትያ (ሰማዕታት)
፫.ቅዱሳት ደናግል አጥራስስ ወዮና (ሰማዕታት)
፬.ቅዱስ አትናቴዎስ የዋሕ

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
፪.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
፫.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)

"እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ። አይታችሁትማል አለው።
ፊልጶስ፦ 'ጌታ ሆይ! አብን አሳየንና ይበቃናል?' አለው። ጌታ ኢየሱስም አለው፦ 'አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል። እንዴትስ አንተ አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አመታምንምን?"
(ዮሐ. ፲፬፥፯-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊት <3

ቆራጧ እናታችን ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ አማኞች ሞገሳችን ናት። እጅግ የሚደነቅ መንፈሳዊ አርበኝነትን በካቶሊኮች ላይ አሳይታለችና።

ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ የተወለደችው በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምሥራቅ ኢትዮጵያ ዳውሮ አካባቢ ነው። ወላጆቿ ባሕር አሰግድና ክርስቶስ ዕበያ ይባላሉ። ክርስትናን በሚገባ አጥንታ አድጋ በወላጆቿ ፈቃድ በሥርዓቱ ባል አገባች። ግን ወዲያው አፄ ያዕቆብ ገደሉባት።

ወላጆቿም ግድ ብለው ሥዕለ ክርስቶስ የተባለ የሱስንዮስን የጦር መሪ አጋቧት። እስከ ሃያ አራት ዓመቷም ልጆችን ወለደች። በዚህ ሁሉ ጊዜ የጾምና የጸሎት ሰው ነበረች። አፄ ሱስንዮስ ተዋሕዶን ክዶ ካቶሊክ በሆነ ጊዜ ባሏ ወደ ንጉሡ እምነት ገባ።

በዚህ ስታዝን ይባስ ብሎ ጠዳ ላይ የአቡነ ስምዓን (ጳጳሱን) ልብስ ግዳይ ይዞ ቀረበ። እርሷም ልቧ ቆረጠ። ፈጣሪ ሦስቱን ልጆቿን አከታትሎ ወሰደ። ደስ ብሏት ጠፍታ ሳጋ (ዛሬ ገዳሟ ያለበት) ገባች። ቀጥላም መነኮሰች።

ከዚህ በኋላ እየዞረች መናፍቃን ስታሳፍር ሕዝቡን ስታጸና ዓመታት አለፉ። በእርሷ ስብከትም ብዙ መነኮሳትና ምዕመናን ሰማዕት ሆኑ። እርሷም በየገዳማቱ ተንከራተተች። በደዌ ተሰቃየች። በንጉሡ ተይዛ ሁለት ጊዜ ወደ በርሃ ተሰደደች።

ፋሲል ነግሦ ሃይማኖት ተመልሶ ሃገር ሲረጋጋ ወደ ምጽሊ ከዚያም ወደ መንዞ መጥታ ገዳም መሥርታ መናንያንን ሰብስባ ስታጽናና ኑራለች። በተወለደች በሃምሳ ዓመቷም በ፲፮፻፴ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ዐርፋ ተቀብራለች። የተጋድሎ ዘመኗም ሃያ ስድስት ዓመታት ናቸው። ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ሰማዕትም ጻድቅም ናት።

የጥቡዓን አምላክ የሊቁን ምሥጢር፣ የቅድስቷን መጨከን ያድለን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፲፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (ፍልሠቱ)
፪.ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊት
፫.አባ ሲኖዳ (ዘደብረ ጽሙና - ጐጃም)
፬.ጻድቃን እለ ወጺፍ
፭.ቅዱሳን አብርሃምና ሐሪክ
፮.ቅድስት ወለተ ጳውሎስና ወለተ ክርስቶስ

ወርኀዊ በዓላት
፩.እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት
፪.ያዕቆብ ሐዋርያ
፫.መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬.አባ ገሪማ
፭.አባ ጰላሞን
፮.አባ ለትጹን
፯.ቅዱስ ኤጲፋንዮስ

"በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።"
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፯-፳፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አኖሬዎስ ጻድቅ (ንጉሠ ሮም)
፪.አባ ዳንኤል ገዳማዊ
፫.ቅዱስ አውሎጊስ መነኮስ
፬.ቅድስት ጣጡስ ሰማዕት
፭.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮.ቅዱስ ኪስጦስ ሰማዕት
፯.ቅዱስ ፊቅጦር ምዑዝ
፰.አባ ዮሐንስ መሐሪ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ
፬.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ

"ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ። በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።"
(፩ዮሐ ፪፥፲፭-፲፯)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.በዓተ ጾመ ነቢያት
፪.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፫.ልደተ ቅዱስ ቂርቆስ
፬.ብጽዕት ኢየሉጣ
፭.አባ ሚናስ ዳግማይ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
፪.ቅድስት እንባ መሪና
፫.ቅድስት ክርስጢና

"አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም፣ በለቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ። አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፣ ቁጣው የዘገየ፣ ምሕረቱም የበዛ፣ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።"
(ኢዮ. ፪፥፲፪-፲፫)

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አባ ዳንኤል ገዳማዊ
፪.አባ መርትያኖስ ካልዕ (ዘጠራክያ)
፫.አባ ዮሐንስ ዘደብረ ቢዘን (ኤርትራ)
፬.ቅድስት ደብረ ቀልሞን

ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፫.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፬.እናታችን ቅድስት ነሣሒት
፭.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
፮.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፯.ቅዱስ ሙሴ መርዓዊ

"ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፣ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፣ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፣ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፣ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፣ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል። ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርገዋል።"
(፩ቆሮ ፲፪፥፱-፲፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

<3 ቅዱስ ጢሞቴዎስ <3

ይህ ቅዱስ አባት በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዘመነ ሰማዕታት የነበረ የእንጽና (ግብጽ) ክርስቲያን ነው። በጐ ሕይወቱን የወደዱ አበው በወቅቱ የከተማዋ ጳጳስ፣ የሕዝቡም እረኛ እንዲሆን መርጠው ሾሙት።

ጊዜው የመከራ በመሆኑ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የከተማው መኮንን ክርስቲያኖችን ይገድል ገባ። ቅዱስ ጢሞቴዎስንም "ክርስትናህን ካልካድክ" በሚል አሠረው። ጠዋት ጠዋት እያወጣም ደሙ እስኪፈስ ድረስ ይገርፈው ነበር። ደቀ መዛሙርቱንም አንድ አንድ እያለ ፈጀበት።

ቅዱሱ ግን በትእግስት ሁሉን ቻለ። በዚህ መካከል ዘመነ ሰማዕታት አልፎ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ነጻ ወጣ። ያን ጊዜም ሕዝቡን ሰብስቦ ጸሎትን አደረገ። "ጌታ ሆይ! ይህንን መኮንን እባክህ ማርልኝ? ያደረገው ነገር ሁሉ ባለ ማወቅ ነውና።"

ይህንን ጸሎት በወሬ ነጋሪ የሰማው ያ መኮንን በጣም ተገርሞ በቅዱሱ ፊት ሔዶ በግንባሩ ተደፋ። "ስጠላህ የወደድከኝ አባት ሆይ! ማረኝ?" አለው። ቅዱስ ጢሞቴዎስም አስተምሮ አጠመቀው። ሁለቱም አብረው ሲጋደሉ ኑረው ዐርፈዋል።

አምላከ ቅዱሳን በረድኤተ መላእክት ጠብቆ በወዳጆቹ ምልጃ ይማረን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ኅዳር ፲፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አእላፍ (ዘጠና ዘጠኙ) ነገደ መላእክት
፪.ቅዱስ አስከናፍር ሮማዊ
፫.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አበው (ሽፍቶች የነበሩ)
፬.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘእንጽና
፭.አባ ዘካርያስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.እግዚአብሔር አብ
፪.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፬.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

"ስለ መላእክትም 'መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ' ይላል።
.....ነገር ግን ከመላእክት 'ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ' ከቶ ለማን ተብሏል?
ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?"
(ዕብ ፩፥፯-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፲፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ
፫.ቅዱሳን ዱራታኦስና ቴዎብስታ
፬.አፄ በዕደ ማርያም ጻድቅ
፭.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
፮.ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
፯.አባ ፊላታዎስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፪.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፫.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
፬.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፭.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
፮.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፯.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ

"በሰማይም ሰልፍ ሆነ። ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፤ አልቻላቸውምም። ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ።"
(ራዕይ ፲፪፥፯-፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

ኅዳር ፲፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ሐና ቡርክት
፪.ቅዱስ አርኬላዎስ ሰማዕት
፫.አባ ኤልሳዕ አበ ምኔት
፬.አባ ጳኩሚስ መነኮስ
፭.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፮.ቅድስት አውራንያ (የሰማዕቱ እናት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
፫.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፬.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

"መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው።
ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል።
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው።
.....ሰው እናታችን ጽዮን ይላል። በውስጥዋም ሰው ተወለደ። እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።"
(መዝ ፹፮፥፩-፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

እንኳን ለቅድስት ሶፍያ እና ለእናቶቻችን ቅዱሳት ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

እስኪ ዛሬ በጥቂቱ የተባረኩ (ቡሩካት) እናቶቻችን እንዘክር። "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል። እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቡርክት እምቡሩካን፣ ኅሪት እምኅሩያን" ናትና።

ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች። ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች። እርሷ እመ ብርሃን፣ የአምላክ እናቱ፣ የሰውነታችን መመኪያ ናትና።

እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት፣ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ" ማለታችን ነው።
፩."ንጽሕት" ትባላለች። ሌሎች ሰዎች (ቅዱሳን) ቢነጹ ከገቢር፣ ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም። እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከኃልዮ ንጽሕት ናት።
"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ - ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው! ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም።" እንዲል።
(ተአምረ ማርያም)
፪."ጽንዕት" እንላታለን። ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው። እመቤታችን ግን "ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ" "ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ" ድንግል ናትና።
"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት።
(ቅዱስ ያሬድ)
ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም - ማርያም ዘላለማዊት ድንግል ናት።" እንዳለ።
(መጽሐፈ ቅዳሴ)
፫.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን። ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው። እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ - የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና።
፬.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን። ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል፣ እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና።

የእመ ብርሃን ይቆየንና ደግሞ ሌሎች ቅዱሳት እናቶቻችንን እንመልከት። እናቶቻችን ስናከብር የምንጀምረው በቅድስት ሔዋን ነው። ብዙ ጊዜ የእናታችን ሔዋን ጥፋቷ እንጂ በጐ ነገሯ፣ ደግነቷ፣ ንስሐዋ አይነገርላትም። ሆኖም እናታችን ቅድስት ሔዋን ክብር የሚገባት ሴት ናት።
ክርስቶስ ሰው የሆነ እርሷንና ልጆቿን ለመቀደስ ነውና።
"ከመ ይስዓር መርገማ ለሔዋን ዲበ ዕፅ ተሰቅለ" እንዲል።
(ድጓ)

ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን እነ ሐይከል፣ እድና፣ ሣራ፣ ርብቃ፣ አስኔት፣ ሲፓራ፣ ሐና፣ ቤርሳቤህን የመሰሉ እናቶቻችን በበጐው መንገድ ፈጣሪን ደስ አሰኝተዋል። በዘመነ ሥጋዌም ቅዱሳቱ ሐና፣ ኤልሳቤጥ፣ ማርያም፣ ሶፍያ፣ ሰሎሜ፣ ዮሐና እና ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በጐነታቸው ያበራል።

ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የተነሱ አእላፍ ቅዱሳት እናቶቻችንን ግን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም።
በቅድስናቸው አራዊትን ያሰገዱ፣ ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ፣ አጋንንትን የረገጡ፣ በዘንዶ ላይ የተጫሙ ብዙ እናቶችን ቤተ ክርስቲያን አፍርታለች።

ዛሬም ቢሆን በበርሃና በከተማ በጐውን ጐዳና የተከተሉ ብዙ እናቶች እንዳሉን እናውቃለን፤ አንድም እናምናለን።
ግን ግን በከተሞች የምንመለከተው ሥርዓቱን የለቀቀው የበርካታ እኅቶቻችን አካሔድ ለሃገርም ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ ስጋት ነው። ክብርና ነውር የማይለይበት ዘመን ይመስላል።

ይህንን እያነበባችሁ ያላችሁ እኅቶቼ! አንድ ነገር
ልንገራችሁ። በመልካቸው ብዙዎችን ያጋጩ፣ አጊጠው በመታየታቸው ብዙዎችን ያሰናከሉ፣ ለብዙ ምዕመናንም የጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሴቶች በታሪክ ነበሩ።

የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ያሉት ከመሬት በታች ነው። አፈር በልቷቸዋል። ስም አጠራራቸውም ጠፍቷል። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ዛሬ በዘላለማዊው እሳት እየተቃጠሉ በሲኦል በጥልቁ ውስጥ አሉ።

እናም ወገኖቼ! ይህን አውቀን እንንቃ። ይህ ዓለም ጠፊም፣ አጥፊም ነውና። እድሜአችን ቢረዝምና ከዚህ በኋላ ለመቶ ዓመታት ብንኖርም እርሱም ማለቁ አይቀርምና። ምርጫችን ዘላለማዊው ሕይወት ይሁን ትላለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን።

<3 እለ ቅድስት ሶፍያ <3

ቅድስት ሶፍያና አብረዋት በዚህ ዕለት የሚከበሩ ቅዱሳት አንስት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም የነበሩ ክርስቲያኖች ናቸው። አብዛኞቹ መልክ (ደም ግባት) ከጠባይ ጋር የተስማማላቸው ነበሩ። ነገር ግን ከምድራዊው ክብር ሰማያዊውን መርጠው ለመንፈሳዊው ሙሽርነት ወደ ገዳም ገቡ።

ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል በጸጋና በሞገስ፣ በትምህርትም የምትበልጥ ቅድስት ሶፍያ ናትና እመ ምኔት አድርገው ሾሟት። እርሷም ለገዳሙ በጐውን ሥርዓት ሠራች። ሁሉም (ደናግሉም መነኮሳይያቱም) በአንድነት ይጾማሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይሰግዳሉ፣ የቅዱሳንን ተጋድሎ ያነባሉ። ሥጋውን ደሙን ይቀበላሉ።

እርስ በርስ ደግሞ ፈጽመው ይፋቀራሉ። በዚህ ሕይወት አንዳንዶቹ እስከ ሰባ ዓመት ቆዩ። የቅድስናቸው ዜና ሲሰማ በሮም ግዛት ያሉ ወጣት ሴቶች እየመጡ ይቀላቀሏቸው ነበር። ቅድስት ሶፍያም የሕይወትን መንገድ ታሳያቸው ነበር።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ከሐዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ለጦርነት ወደ ፋርስ ሲሔድ ስላያቸው ባንድነት ሰብስቦ ሁሉንም በሰይፍ አስመታቸው። ቅድስት ሶፍያም አብራ ሰማዕት ሆነች። ስለ ቅዱሳኑ የሚበቀል ጌታም ቅዱስ መርቆሬዎስን ልኮ በጦርነቱ መካከል በጦር ወጋው። ዑልያኖስ ወደ ዘላለም ኩነኔ ሲሔድ ቅዱሳት አንስት ወደ ገነት ሔደዋል።

<3 ባሕረ ሐሳብ <3

ዳግመኛ በዚህ ቀን በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባሕረ ሐሳብ በዓለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን አግኝቷል። ሊቁ ቅዱስ ድሜጥሮስ (የግብጽ አሥራ ሁለተኛ ፓትርያርክ) መንፈስ ቅዱስ ቀመረ ባሕረ ሐሳብን ገልጾለት በዓለም ላሉ ሊቃነ ጳጳሳት ልኮላቸው በዚህች ዕለት በሮም ከተማ ተሰበሰቡ።

ሊቃውንትም ሐዋርያት ካስተማሩት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ቢያገኙት በደስታ ተቀብለውታል። እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ ክርስቲያን እየተገለገለችበት ይገኛል።

የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ ዛሬም እንደ እነርሱ ያሉትን አያሳጣን። በጸሎታቸው ምሮ ከበረከታቸው ይክፈለን።

ኅዳር ፲ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፪.ደናግለ ሮሜ (ሰማዕታት)
፫.ቅዱስ ጳውሎስ ሰማዕት
፬.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ
፭.ጉቡዓን ኤጲስ ቆጶሳት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
፭.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
፮.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
፯.ቅዱስ እፀ መስቀል

"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን
በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።"
(፩ጴጥ ፫፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Читать полностью…
Subscribe to a channel