"አባቴ ጊዮርጊስ ሆይ! የልቤን ኀዘን ስነግርህ ፈጥነህ ጸሎቴን ስማኝ፤ ነገሬንም አድምጠኝ።
ያዘኑትን የምታረጋጋ ሆይ ወደ እኔ ቅረብ፤ በአጠገቤም ተገኝተህ አለሁልህ በለኝ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
"ከወርቅና ከብር ይልቅ ሞገሱ የሚበልጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረሱ እኛን ለመርዳት ይምጣ፤ ይመላለስም።"
(ስብሐተ ፍቁር ዘጊዮርጊስ)
"ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! በአፌ ብቻ ሣይሆን ከልቤ እወድሃለሁና ሰላም እልሃለሁ።
ስለዚህ አባት ሆይ! ምስጋናዬን አታቃልብኝ ተቀብለህ ዋጋዬን አሰጠኝ እንጅ። ለእኔ የድሃው ንጹሕ ወርቄ አንተ ጊዮርጊስ ነህና።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
እንኳን አደረሳችሁ!
‹‹ኦ ፍጡነ ረድኤት እምሩጸተ ነፋስ
ወዐውሎ ለዘይጼውዓከ በተወክሎ
ጊዮርጊስ ቅረብ ለምሕረት ወለተሣህሎ፡፡
ተወከፍ ወትረ ጸሎትየ ወቃለ ጽራኅየ ኵሎ፡፡ እስመ ልበ አምላክ ርኅሩኅ በኀቤከ ሀሎ፡፡››
"ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! አንተን በመታመን ለጠራህ ሁሉ ፈጥነህ ስትደርስለት ከዓውሎ ነፋስ ይልቅ በተፋጠነ ሩጫ ነው እኮን፡፡
ጊዮርጊስ ሆይ! የዘወትር ጸሎቴንና የቃሌንም የልመና ጩኸት ትቀበል ዘንድ ለይቅርታና ለምሕረት ፈጥነህ ወደ እኔ ቅረብ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
"አባቴ ጊዮርጊስ ሆይ! የልቤን ኀዘን ስነግርህ ፈጥነህ ጸሎቴን ስማኝ፤ ነገሬንም አድምጠኝ።
ያዘኑትን የምታረጋጋ ሆይ ወደ እኔ ቅረብ፤ በአጠገቤም ተገኝተህ አለሁልህ በለኝ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
"ዘወትር በማይጠልቅ በብሩህ ፀሐይ ፊት በምድር ዳርቻዎች ሁሉ የስምህ ባለሟልነት የደረሰ የአእላፍ ሰማዕታት አለቃቸው ሰላምታ ለአንተ ይገባል።
ክንፈ ፈጣን ከራድዮን ዖፍ የተባልህ ጊዮርጊስ ሆይ የአፍ እስትንፋስን ተቀብለህና ተሸክመህ ሕማሜን በትን።"
(ሊቁ አርከ ሥሉስ)
በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዛሬ (ጥር ፪ ቀን) የታላቁ ቅዱስና ሊቀ ሰማዕታት ማር ጊዮርጊስ የልደት በዓሉ ነው፡፡
የማር ጊዮርጊስ በረከቱ ይደርብን፡፡
<3 ዕለተ ጌና <3
ከሳምንታት በፊት ጀምረን የክርስቶስን የማዳን ሥራ ለመገንዘብ እየሞከርን ቆይተናል። በተለይ ታኅሣሥ ፯ ቀን "ስብከት" በሚል ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን ትንቢት መነገሩን፣ ምሳሌ መመሰሉን፣ ሱባኤ መቆጠሩን ተመልክተን ነበር።
ቀጥለን ደግሞ ታኅሣሥ ፲፬ ቀን "ብርሃን" በሚል አምላካችን እንደ ምን ባለ ጥበቡ ብርሃኑን እንደ ሰጠን አንድም ወደን ወደ ጨለማ በገባን ጊዜ ሥጋችንን ተዋሕዶ ብርሃን እንደ ሆነልን ለማየት ሞክረናል።
ታኅሣሥ ፳፩ ቀን ደግሞ በበደላችን ምክንያት የነፍሳችንን እረኛ አጥተን ነበር። ለእኛው በደል እርሱ ክሶ ድጋሜ መልካም እረኛችን ሆኖ በሥጋ ማርያም መገለጡን አየን። የዛሬው በዓል ዕለተ ጌና ደግሞ ማሠሪያው ነው።
"ጌና" ማለት በቁሙ "ዕለተ ልደት ስቡሕ ማለትም አምላክ ሰው የሆነበት ምስጉን ቀን" እንደ ማለት ነው። ይህ ቀን ሁሌም በየዓመቱ "አማኑኤል (ጌና)" እየተባለ ይከበራል። ምክንያቱ ደግሞ ጌታ የተጸነሰ መጋቢት ፳፱ ቀን በመሆኑና ከዚህ ቀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ብንጨምር ይህ ዕለት ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ይመጣል።
ነገር ግን በአራተኛው ዓመት ዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜን ስድስት ስትሆን ዘጠኝ ወር ከስድስት ቀን ስለሚሆን ቀኑን እንዳይለቅ በዘመነ ዮሐንስ ዕለተ ልደቱ ለክርስቶስ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ይከበራል። ያም ሆኖ በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ ፳፰ን አክብረናል ብለን ፳፱ን አንተወውም። እርሱም ይከበራል።
በዚያው ልክ ደግሞ በሦስቱ አዝማናት (በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ) ልደቱ ታኅሣሥ ፳፱ ነው ብለን ፳፰ን አንሽረውም። "ጌና - አማኑኤል - ዕለተ ማርያም" እያልን እናከብረዋለን እንጂ። ብዙ ጊዜም በተለምዶ በዓለ ልደትን "ጌና" በማለት ፈንታ "ገና" የምንል ብዙዎች አለን።
ግን አበው ባቆዩልን ትውፊት "ጌና" ልደቱን የሚመለከት ሲሆን "ገና" ግን ባሕላዊ ጨዋታውን የሚመለከት ቃል ነው።
<3 ዕለተ ማርያም <3
ዳግመኛ ይህ ቀን ዕለተ ማርያም ይባላል። "ማርያም" የሚለው ቃል ብዙ ትርጉምን ያዘለ የእናታችንና የእመቤታችን፣ የተስፋችንና መመኪያችን የድንግል እመ ብርሃን ስም ነው።
ክርስቶስ ተጸነሰ፣ ተወለደ ስንል ለዚህ ሁሉ ምሥጢር ማካተቻና የድኅነታችን መጀመሪያ፣ የመመኪያችን ዘውድና የንጽሕናችን መሠረት ድንግል ማርያም ናትና ከፈጣሪ ቀጥሎ ታላቅ ክብር፣ ምስጋና፣ ስግደትና ውዳሴ ለእርሷ ይገባታል። መድኅናችን ክርስቶስ ያዳነን በእርሷ ምክንያት ነውና።
ሠለስቱ ምዕት (ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት) ይህንን ምሥጢር ሲያደንቁ እንዲህ ብለዋል፦
በሥጋ ማርያም ጌታ ተጸነሰ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ተወለደ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ አደገ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ተጠመቀ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ አስተማረ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ተሰቀለ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ሞተ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ተነሳ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ዐረገ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ፤
በሥጋ ማርያም ጌታ ዳግመኛ በሕያዋንና ሙታን ላይ ይፈርድ ዘንድ ከመለኮቱ ኃይል ጋር ይመጣል።
(መጽሐፈ ቅዳሴ)
ለድንግል ማርያም ክብርና ውዳሴ ከስግደት ጋር ይሁን!
የድንግል ማርያም ልጅ አማኑኤል ክርስቶስ በርኅራኄው ይማረን። ከበረከተ ልደቱም ያሳትፈን።
ታኅሣሥ ፳፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
፩.አማኑኤል አምላካችን
፪.በዓለ ጌና ስቡሕ
፫.ዕለተ ማርያም ድንግል
፬.መቶ ሰባ አራት ሰማዕታት (የቅዱስ ጳውሎስ ማኅበር)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱሳን (አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ)
፪.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፫.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፬.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
፭.ቅዱስ አባዲርና ቅድስት ኢራኢ
"የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርስዋ የተጸነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች። እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ 'እነሆ ድንግል ትጸንሳለች። ልጅም ትወልዳለች። ስሙንም አማኑኤል ይሉታል።' የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።"
(ማቴ ፩፥፳-፳፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ታኅሣሥ ፳፯ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አብሳዲ ሰማዕት
፪.አባ አላኒቆስ ሰማዕት
፫.አባ በግዑ ጻድቅ
፬.አባ ፊልጶስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
፪.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
፫.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
፬.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፮.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል። ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ።' ይላቸዋል። እላችኋለሁ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።"
(ሉቃ ፲፭፥፫-፯)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
<3 ቅድስት አንስጣስያ <3
ይህች ቅድስት እንደ በርካቶቹ ቅዱሳት እናቶቻችን ሁሉ የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ናት። በቀደመችው ታናሽ እስያ አካባቢ ተወልዳ የነገሥታት ዘር በመሆኗ ያደገችው በቤተ መንግሥት ነው። አባቷ ከክቡራኑ አንዱ ቢሆንም ሙያው ጣዖትን ማምለክ ነበር።
ጊዜው የመከራ በመሆኑ ብዙ ሴቶች የሚኖሩት ክርስትናቸውን ደብቀው ነው። ከእነዚህ መካከል አንዷ ደግሞ የቅድስት አንስጣስያ እናት ናት። ማንን እንደምታመልክ አረሚ ባሏ አያውቅም ነበር።
አንስጣስያን በወለደች ጊዜም በድብቅ አስጠመቀቻት። ከሕፃንነቷ ጀምሮም ፍቅረ ክርስትና እንዲያድርባት ነገረ ሃይማኖትን አስተማረቻት። ቅድስት አንስጣስያ ወጣት በሆነች ጊዜ ግን ከውበቷ የተነሳ ተመልካቿ በዛ። እርሷ ግን ይህ ሁሉ የዓለም ኮተት አይገባትም ነበር።
በፈጣሪዋ ፍቅር ከመጠመዷ የተነሳ ለመሰል ነገሮች ትኩረት አልነበራትም። ትጾማለች፣ ትጸልያለች፣ ነዳያንና እሥረኞችን ትጐበኛለች። በዚህም ዘወትር ደስ ይላት ነበር። ነገር ግን አባቷ ባላሰበችው ጊዜ ለአንድ አረማዊ አጋባት። በጣም አዘነች ግን ተስፋ አልቆረጠችምና መፍትሔ ፈለገች።
ድንግልናዋን እንዳያረክስ በጫጉላዋ ቀን ታመምኩ ብላ ተኛች። ከዚያ በኋላም አንዴ በልማደ አንስት አንዴ በሕመም እያመካኘች አላስቀርብ አለችው። እርሱ የጦር አለቃ በመሆኑ ወደ ጦርነት ሲሔድ እርሷ ታጥቃ ስለ ቀናች እምነት የታሠሩ ክርስቲያኖችን ታገለግል ነበር።
ቁስላቸውን እያጠበች አንጀታቸውን በምግብ እየደገፈች ደስ ታሰኛቸውም ነበር። ባሏ ሲመለስ ግን ይህንን በመስማቱ ድጋሚ እንዳትወጣ ቆልፎባት ወደ ጦርነት ተመለሰ። ፈጽማ ስላዘነችበትም እግዚአብሔር በጠላቶቹ እጅ አሳልፎ ሰጠውና ሞተ።
እርሷም ከነ ድንግልናዋ ቀሪ ሕይወቷን ስትመራ መከራው ወደ እርሷ ደረሰ። ተይዛ ቀርባ በአረማውያን እጅ ብዙ ተሰቃየች። በዚህች ቀንም ስለ ክርስቶስ ተገድላ ክብረ ሰማዕታትን ተቀዳጀች።
<3 ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ <3
ቅዱሱ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የክርስቶስን ሕማማት ለመሳተፍ ሲተጉ ከኖሩ ጻድቃን አንዱ ነው። መሉ ጊዜውን በበርሃ ሲያሳልፍ ብዙ ተጋድሎን ፈጽሟል። በተለይ ሲጸልይ እግሩን ከዛፍ ላይ አስሮ ቁልቁል ከባሕር ውስጥ ሰጥሞ ነው። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ዕረፍቱን ታስባለች።
አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን ክብሩን ያድለን። ከወዳጆቹ በረከትም አይለየን።
ታኅሣሥ ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት
፪.ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ
፫.ቅድስት ዮልያና ሰማዕት
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።"
(፩ጴጥ ፫፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
<3 አባ ዮሐንስ ከማ <3
ቅዱስ ዮሐንስ ከማ በዘመነ ጻድቃን (በተለይም በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ከተነሱ አበው አንዱ ነው። ቅዱሱ ድንቅ ሕይወት ስለ ነበረው በዜና አበው በስፋት ተጠቅሷል። መጽሐፈ ስንክሳር "ከማ" የሚለውን ቃል "ከማ ብሒል ካም - 'ከማ' ማለት 'ካም' ማለት ነው" ይላል።
"ካም" የሚለው ቃል ደግሞ ብዙ ጊዜ መልካቸው ጠቆር ላሉ ሰዎች የሚሰጥ ስም ነው። ምናልባት የድሮ የኢትዮጵያ ግዛት በነበረው ደቡብ ግብጽ የነበረ አባት እንደ መሆኑ የዘር ሐረጉ ከኢትዮጵያ የተመዘዘ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
ቅዱሱ በስፋት የሚታወቀው በድንግልና ሕይወቱ ነው። መልካም ቤተሰቦቹ በሥርዓት አሳድገው "እንዳርህ" አሉት። እንቢ ቢላቸው ብቸኛ ልጃቸው ነውና ፈጽሞ ሊያዝኑበት ነው። ደስታውን ለቤተሰቦቹ ሰውቶ በተክሊል ተዳረ።
እርሱ የሚሻው በድንግልና መኖርን ነውና ጥበበኛ እግዚአብሔር ሚስቱ የተቀደሰች እንድትሆን አደረጋት። በሠርጋቸው ምሽት ቅዱስ ዮሐንስ ከማ መልከ መልካሟን ሙሽራ በድንግልና ይኖሩ ዘንድ ቢጠይቃት በደስታ አነባች።
ምክንያቱም እርሷም ያገባችው ቤተሰብን ለማስደሰት እንጂ ፈቃዷ በድንግልና መኖር ነበርና። ሁለቱም ስላደረገላቸው ፈጣሪን እያከበሩ የድንግልና ሕይወት ተጋድሎን ቀጠሉ። ቅዱሳኑ በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ አንዲት ምንጣፍን እያነጠፉ አንድ ልብስንም በጋራ ለብሰው እያደሩ ድንግልናቸውን ጠበቁ።
አምላከ ድሜጥሮስም ቅዱስ መልአኩን ልኮላቸው በመካከላቸው ያድር ክንፉንም ያለብሳቸው ነበር። ክብራቸውን ይገልጥ ዘንድም በቤታቸው መካከል ታላቅ ዛፍን ያለ ማንም ተካይነት አበቀለ።
በዚህ ጊዜ ግን ቅዱስ ዮሐንስ ከማ ድንግሊቱን ሚስቱን "የከተማ ኑሮ ይብቃን፤ ወደ በርሃ እንሒድ።" አላት። እርሷም "ፈቃድህ ፈቃዴ ነው።" ስላለችው እርሷን ወደ ደናግል ገዳም አስገብቶ እርሱ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ተጓዘ።
ቅድስቲቱ አስቀድማ ጸጋው በዝቶላት ነበርና ድውያንን ትፈውስ ነበር። የገዳሙ እመ ምኔት ሆና መርታ በክብር አረፈች። ቅዱስ ዮሐንስ ከማም በቅዱስ መልአክ መሪነት መጀመሪያ ወደ አባ ዳሩዲ ሔዶ መነኮሰ።
በመጨረሻም በቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ገዳም ጐን ማደሪያን አነጸ። በዚያም በመቶ የሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርትን አፍርቶ በአበ ምኔትነት አገለገለ። ለእመቤታችንና ለቅዱስ አትናቴዎስ ልዩ ፍቅር የነበረው ቅዱሱ ከበርካታ የቅድስና ዘመናት በኋላ በዚህች ቀን በክብር ዐርፎ ተቀብሯል።
አምላከ ቅዱሳን ይራዳን፣ ይባርከን፣ ይቀድሰን። ከወዳጆቹ በረከትም ያሳትፈን።
ታኅሣሥ ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱሳን አምስቱ መቃብያን
፪.ቅዱስ ዮሐንስ ከማ እና የተቀደሰች ሚስቱ
፫.ቅዱስ ዳንኤል መነኮስ
፬.ቅዱስ ኒቆላዎስ መኮንን
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፮.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
፯.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ
"ቃሌን የሚጠብቅ በትእዛዜም ጸንቶ የሚኖር በረከቴን የሚያገኝ በእኔ ዘንድ የሚከብር እርሱ ነው።
ቃሌን የሚጠብቅ በትእዛዜም ጸንቶ የሚኖር ሰው ሁሉ ከምድር የተገኘውን ድልብ ይበላል። ቅን ልቡና ያላቸው ደጋጎች ነገሥታት ወደ ገቡበት ወደ ገነትም ገብቶ ይኖራል።"
(፩መቃ ፲፪፥፵፫-፵፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
"ሰላም ለልደትከ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያ
ለሰብአ ግብጽ ወኢትዮጵያ
ሞገሰ ልደትከ አባ በአዕይንትያ ርእያ
ነፍስየ ትባርኮሙ ወታስተብፅዎሙ ነያ
ለጸጋ ዘአብ ወእግዚእ ኀረያ"
(ለኢትዮጵያና ለግብጽ ሰዎች ሐዋርያ የሆንክ ተክለ ሃይማኖት ለልደትህ ሰላምታ ይገባል።
የልደትህን ክብር በዓይኖቿ ዓይታ ሰውነቴ አባትህ ጸጋ ዘአብንና እናትህ እግዚእ ኀረያን እነሆ ታመሰግናቸዋለች፤ ከፍ ከፍም ታደርጋቸዋለች።)
(ነግሥ)
እንኳን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ቅዱስ አግናጥዮስ እና ቅድስት አስቴር ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ <3
<3 ልደት <3
መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው። እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ፣ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል።
በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል። በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል።
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ ቀን በ፲፪፻፮ ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን በ፲፪፻፯ ዓ/ም ነው። በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል። ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል።
<3 ዕድገት <3
የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል። ይህንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል። በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት፣ ሐዲሳትን) ተምረዋል። በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል። ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል።
<3 መጠራት <3
አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ።
የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ። "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን። ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ። ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በግርማ ዐረገ። ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም። ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ።
<3 አገልግሎት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ። በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ሁለት መልክ ነበራት።
፩ኛ.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል።
፪ኛው. ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር።
ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ። ሕዝቡንና መሳፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል።
<3 ገዳማዊ ሕይወት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል። እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በሦስት ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል።
እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለአሥራ ሁለት ዓመታት፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለሰባት ዓመታት፣ በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለሰባት ዓመታት በአጠቃላይ ለሃያ ስድስት ዓመታት አገልግለዋል።
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለሃያ ሁለት ዓመታት ቆመው ጸልየዋል። በተሰበረ እግራቸውም ስድስት ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለሰባት ዓመታት ጸልየዋል።
<3 ስድስት ክንፍ <3
ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል። ጻድቁ ምድረ እስራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ፣ እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር።
የወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው። ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር።
ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም። በገሃድ፦
በቤተ መቅደስ ብስራቱን፣
በቤተ ልሔም ልደቱን፣
በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣
በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣
በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር።
የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ።
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አባታችንን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው።
በዚያም፦
የብርሃን ዓይን ተቀብለው፣
ስድስት ክንፍ አብቅለው፣
የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣
ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣
ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው፣
ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል።
<3 ተአምራት <3
የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው።
ሙት አንስተዋል፣
ድውያንን ፈውሰዋል፣
አጋንንትን አሳደዋል፣
እሳትን ጨብጠዋል፣
በክንፍ በረዋል፣
ደመናን ዙፋን አድርገዋል።
ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል። በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል። በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና።
<3 ዕረፍት <3
ጻድቅ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው፣ መከራን በብዙ ተቀብለው፣ እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ ቀን በ፲፫፻፮ ዓ/ም ዐርፈዋል። ጌታ፣ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል። አሥር ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል።
<3 ዳዊትና ጽዮን <3
ቅዱስ ዳዊት ጽዮንን አንጾ ጽላተ ኪዳኑን አመጣ። ለአምላከ ያዕቆብ ማደሪያን ሊፈልግም ዓይኑ ከእንቅልፍ ተከለከለ።
(መዝ. ፻፴፩፥፪)
የፈጣሪውን ፈቃድ ሊጠይቅ ሱባኤ ቢገባ "አኮ አንተ ዘትነድቅ ሊተ ቤተ - አንተ ሳትሆን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው።" አለው።
አያይዞም የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር ቢገልጥለት "ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ - እነሆ በኤፍራታ ሰማነው።" ሲል ተናግሯል።
(መዝ. ፻፴፩፥፮)
የኪዳኑ ጽላት (ጽዮን) ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ከዙፋኑ ወርዶ ከተራው ሕዝብ ጋርም ተቀላቅሎ በበገናና በመሰንቆ ተጫወተ።
ስለ ፈጣሪው ክብሩን ተወ። ከዳን እስከ ቤርሳቤህ የሚገዛ ኃያል ንጉሥ ነበርና። በጽዮን ፊት እየወደቀ እየተነሳ፣ እየታጠቀ እየፈታ ሲዘምርም ሚስቱ ሜልኮል ናቀችው። እግዚአብሔር ግን ከፍ ከፍ አደረገው።
(፪ሳሙ. ፮፥፲፮)
<3 ክብረ ዳዊት <3
እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል ኢየሩሳሌምን ብዙ ጊዜ ታድጓል። ሰሎሞንና ሕዝቅያስን (ነገሥታቱን) ይቅር ያላቸው ስለ ባለሟሉ ስለ ዳዊት ነው።
የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቃል "የዳዊት ልጅ....." የምትል ናት።
(ማቴ. ፩፥፩)
ጌታችን "ወልደ ዳዊት" መባልን ወዷልና። እንዲያውም ራሱ "እኔ የእሴይ ሥርና የዳዊት ዘር ነኝ።" ሲል ተናግሯል።
(ራእይ ፳፪፥፲፮)
<3 ዕረፍት <3
ነቢየ ጽድቅ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስራኤልን ለአርባ ዓመታት መርቶ አረጀ። "ምነው ያ ኃያል የእግዚአብሔር ሰው ቶሎ አረጀ?" ቢሉ ከገድሉ ጽናት ሰውነቱ ተቀጥቅጦ ነበርና።
በዚያውም ላይ አንድ ቀን ስለ ሕዝበ እስራኤል ቤዛ ይሆናቸው ዘንድ በቀሳፊ መልአክ ፊት ቆሞ ነበርና (ዜና. ፳፩፥፲፮) ሰውነቱ ደከመ። በዚህ ጊዜም ልጁን ሰሎሞንን አንግሦ በሰባ ዓመቱ ከክርስቶስ ልደት ሺህ ዓመታት በፊት ዐርፏል።
<3 ዳዊት በሰማይ <3
በራእየ ጐርጐርዮስ እንደ ተጻፈው ቅዱስ ዳዊትን በሰማይ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ከበውት ያመሰግናል። ከእርሱ ዝማሬ ግርማ የተነሳ የሰማያት ግዘፋቸው ይናወጻል። በገድለ አቡነ ኪሮስ እንደ ተጻፈው ደግሞ ቅዱሳን ነፍሳቸው ከሥጋቸው የምትለየው በዳዊት በገና ጣዕመ ዝማሬ ነው።
በነገረ ማርያም ትምህርት ደግሞ የቅዱስ ዳዊት ቤቱ ከልዑል አምላክ መንበር ሥር ነው።
እንግዲህ ምን እላለሁ! ስለ ቅዱስ ዳዊት ከዚህም በላይ መጻሕፍት ብዙ ይላሉ። ክብሩ ታላቅ ነውና።
በእውነት፣ በእውነት፣ በእውነት ያለ ሐሰት ለዳዊት ክብርና ምስጋና ይገባል!
አምላከ ዳዊት ስለ ከበረው ቃል ኪዳኑ ይማረን። ከንጹሕ አምልኮው ይክፈለን። በዝቶ ከተረፈ በረከቱም አይለየን።
ታኅሣሥ ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ
፪.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፫.አባ ሳሙኤል ጻድቅ
፬.አባ ስምዖን ጻድቅ
፭.አባ ገብርኤል ጻድቅ
፮.አባ ይስሐቅ ጻድቅ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፪.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እስራኤል)
፫.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
"ከሕዝቤም የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ።
ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት። ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት።
እጄም ትረዳዋለች። ክንዴም ታጸናዋለች።
ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም። የዓመጻ ልጅም መከራ አይጨምርበትም።
ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ። የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ።"
(መዝ ፹፰፥፲፱-፳፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
"ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ እምዕንቈ ባሕርይ ዘየሐቱ
ዘተጽሕፈ ብኪ ትእምርተ ስሙ ወተዝካረ ሞቱ
አክሊለ ጽጌ ማርያም ለጊዮርጊስ ቀጸላ መንግሥቱ
አንቲ ኲሎ ታሰግዲ ሎቱ
ወለኪኒ ይሰግድ ውእቱ።"
(የስሙና የሞቱ መታሰቢያ ባንቺ የተጻፈብሽ የሚያበራ ከሆነ ዕንቈ ባሕርይ ይልቅ የጠራ ወርቅ ክበብ ያለው የራስ ቊር የተባለ የጊዮርጊስ የመንግሥቱ የራስ ልብስ ጌጥ ሽልማት የአበባ አክሊል ማርያም ሆይ አንቺ ለእርሱ ሁሉን ታሰግጅለታለሽ (ታንበረክኪለታለሽ) እርሱ ግን ላንቺ ይሰግዳል።)
(አባ ጽጌ ድንግል)
"ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ።"
(ቅዱስ ኤፍሬም)
እንኳን ለታላቁ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
"አስተጋይድ ፈረሰከ ወአብድር እምዐውሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ለከ ይብለከ ልሣነ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት"
(ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዓውሎ ነፋስ ይልቅ ፈረስህን አቀዳድም ይልሃል የንጉሠ ነገሥት ምኒልክ አንደበት።)
እንኳን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
"አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት።"
(አባ ሕርያቆስ)
እንኳን ለቅድስት ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
‹‹ኦ ፍጡነ ረድኤት እምሩጸተ ነፋስ
ወዐውሎ ለዘይጼውዓከ በተወክሎ
ጊዮርጊስ ቅረብ ለምሕረት ወለተሣህሎ፡፡
ተወከፍ ወትረ ጸሎትየ ወቃለ ጽራኅየ ኵሎ፡፡
እስመ ልበ አምላክ ርኅሩኅ በኀቤከ ሀሎ፡፡››
"ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! አንተን በመታመን ለጠራህ ሁሉ ፈጥነህ ስትደርስለት ከዓውሎ ነፋስ ይልቅ በተፋጠነ ሩጫ ነው እኮን፡፡
ጊዮርጊስ ሆይ! የዘወትር ጸሎቴንና የቃሌንም የልመና ጩኸት ትቀበል ዘንድ ለይቅርታና ለምሕረት ፈጥነህ ወደ እኔ ቅረብ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
"ክቡሩ አባት ሆይ! ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብን ግለጽልኝ። ይልቁንም የጸሎትህ ኃይለ ቃል ረዳቴ በመሆን ዓሥራት በኩራት አድርጎ ይጠብቀኝ።"
(መልክአ ገብረ መንፈስ ቅዱስ)
እንኳን ለቅዱስ አምላካችን አማኑኤል፣ ዕለተ ማርያም እና ዕለተ ጌና ስቡሕ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ አማኑኤል <3
የክርስትና ሃይማኖት እጅግ ብዙ ምሥጢራትን ያካትታል። ታላቅ መዝገብ ነውና። ሰዎች እናልፋለን። ዓለምም ታረጃለች እንጂ ምሥጢረ ክርስትና አያረጅም። እዚህ ቦታ ላይ ይጠናቀቃልም አይባልም።
"አማኑኤል" የሚለውን ስም መረዳት የሚቻለው በአንድ መንገድ እርሱም ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን ጠንቅቆ በመማር ነው። ምሥጢራት ደግሞ በእምነት ለማይኖር በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም።
እግዚአብሔር አንድም ነው፤ ሦስትም ነው። ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነቱ፤ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው።
ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው። ዓለምን ከፈጠረ በኋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምህርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው።
ይኸውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው። ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርህ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ። እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ፦
ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው። ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ባለቤቱ ያውቃል።
እግዚአብሔር በኋለኛው ዘመን ሰው የሆነበት ምሥጢር እኛን ለማዳን ቢሆንም ይሔው ተግባሩ ዓለም ሳይፈጠር ያሰበው እንጂ በአዳም ውድቀት ምክንያት ድንገት የታሰበ አይደለም።
እግዚአብሔር አዳምን በሰባት ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በኋላ ግን ንስሐ ስለ ገባ "ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው።
ከዚህ በኋላ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር፣ ሱባኤ ይቆጠር፣ ምሳሌም ይመሰል ገባ።
ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ።
ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሳፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል።
ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት /ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል።
ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል። እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል። መድኅን ክርስቶስም ተወልዶ አድኗቸዋል።
"አማኑኤል" የሚለው ቃል ከዕብራይስጥ ልሳን (ከጽርዕ የሚሉም አሉ።) በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም "እግዚአብሔር ምስሌነ - እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ።" እንደ ማለት ነው።
(ኢሳ. ፯፥፲፬ ፣ ማቴ. ፩፥፳፪)
ምሥጢሩ ግን ከዚህ የሠፋ ነው።
"አማኑኤል" ማለት "እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋን ከነፍሳችን ነፍስን ነስቶ በፍጹም ተዋሕዶ እኛን መሰለን።" ማለት ነው። በሌላ አነጋገርም "አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ።" እንደ ማለት ነው።
ይህንን ሲያደንቁ ቅዱሳን ሊቃውንት "ወዝንቱ ስም ዓቢይ ወኢይደሉ ፈሊጦቶ - ይህ ስም ታላቅ ነው። ወደ ሁለት ሊከፍሉት (ሊለዩት) አይገባም።" ብለው ምሥጢረ ተዋሕዶን አስረድተዋል።
(ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ)
ስለዚህም ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ እኛን ያድን ዘንድ በተለየ አካሉና በከዊነ ቃልነቱ ፍጹም የድንግል ማርያምን ሥጋ ተዋሕዶ የሰውነትንም የአምላክነቱንም ሥራ ሠርቶ አድኖናል።
በማኅጸነ ድንግል ከተቀረጸባት ደቂቃ ጀምሮም ፍጹም ተዋሕዶን ፈጽሟልና መቼም መች አምላክም፣ ሰውም ነው እንጂ ወደ ሁለትነት ማለትም አምላክን ለብቻ ሰውን ለብቻ አናደርግም።
ስለዚህም ዛሬም ዘወትርም እግዚአብሔር ቃል የተዋሐደው ሥጋችን በዘባነ ኪሩብ ሲሠለስና ሲቀደስ ይኖራል። እርሱ ጌታችን እስከዚህ ድረስ ወዶናልና።
ፈጣሪያችን በሦስትነቱ ሥላሴ (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) በአንድነቱ እግዚአብሔር፣ ኤልሻዳይ፣ አልፋ፣ ወዖ፣ ቤጣ፣ የውጣ፣ ኦሜጋ..... እያልን እንደምንጠራው ሁሉ በሥጋዌው ምክንያት አማኑኤል፣ መድኃኔ ዓለም፣ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ እያልን እንጠራዋለን።
እንኳን ለሰማዕቱ አባ አብሳዲ እና ለጻድቁ አባ በግዑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ አባ አብሳዲ <3
ቅዱሱን የመሰሉ አባቶች "መስተጋድላን" ይባላሉ። ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው። መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው።
ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ። ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ። የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከሁለት አካላት ጋር ነው። በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖታችሁን ካዱ፤ ለጣዖትም ስገዱ።" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው።
በተለይ ሁለተኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል። የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ።
ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ። ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ። ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል።
ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል። ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው። ፍቅረ መስቀሉን የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም።
ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው። ጌታችን "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ።" (ማቴ. ፲፮፥፲፰) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን።
ቅዱስ አባ አብሳዲ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። እንደርሱ በቅድስና ያጌጠ ባልንጀራም ነበረው። ስሙም ቅዱስ አላኒቆስ ነበር።
እነዚህ ክርስቲያኖች በዚያ የመከራ ዘመን ግራ ቀኝ ሳይሉ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን ጠንቅቀው ተምረዋል። በጐውን ጐዳና አጽንተው በመገኘታቸውም መንፈስ ቅዱስ ሁለቱንም በአንዴ ለእረኝነት ጠራቸው።
ጵጵስና ከዚህ በፊት እንደ ተመለከትነው እዳ (ኃላፊነት) እንጂ ምድራዊ ክብርን ማጋበሻ መንገድ ወይም የሥጋ ድሎትን መፍጠሪያ ዙፋን አይደለም። ያም ሆኖ ምርጫው የመንፈስ ቅዱስ ሲሆን ደስ ያሰኛል።
በእርግጥም የክርስቶስን መንጋ እንደሚገባ መምራትና በለመለመው የወንጌል መስክ ማሰማራት የሚያስገኘው ክብር በሰማያት ታላቅ ነው። ያም ቢሆን ግን ከብዙ መከራ በኋላ እንጂ እንዲሁ በዋዛ አይደለም። የእግዚአብሔር ጸጋውና መንግሥቱ ያለ መከራ አትገኝምና።
ቅዱሳኑ አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስም ይህንን ኃላፊነት የተረዱ ነበርና ታጥቀው ሥራቸውን ጀመሩ። እንደ ሐዋርያት ሥርዓትም ያላመነውን ማሳመን፣ ያመነውን በሃይማኖቱ ማጽናት፣ የጸናውን ደግሞ ለምሥጢራተ ቅድሳት (ሥጋ ወደሙ) ማብቃት የዘወትር ተግባራቸው ነበር።
ቅዱሳኑ በዚህ ተጋድሏቸው ሳሉ ዜናቸው በየቦታው ተሰማ። ነገር ግን ይህ ዝናቸው የወለደው መከራን ነበር። በጊዜው አውሬው ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን ከዋሉበት አላሳድር ካደሩበትም አላውል ብሎ ነበር።
ለክፋቱ እንዲመቸው በየሃገሩ ጨካኝ መኮንኖችን ሾመ። በምድረ ግብጽም ሁለት ገዢዎችን ሲያኖር አንዱ አርያኖስ (በኋላ አምኖ ሰማዕት ሆኗል።) ሁለተኛው ደግሞ ሔርሜኔዎስ ይባላሉ።
እነዚህ መኳንንት ግብጽን ለሁለት ተካፍለው በሥራቸው ገዥዎችን ሹመው በግፍ ተግባራቸው ክርስቲያኖችን ይቀጡ ገቡ። የስቃይ ተራው ደግሞ የሁለቱ ቅዱሳን (አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስ) ነበርና ተከሰሱ።
ለፍርድ ይቀርቡ ዘንድም አርያኖስ በማዘዙ ወታደሮች መጡ። ነገሮችን አስቀድሞ የሚያውቀው ቅዱስ አብሳዲም ምንም ስለ ክርስቶስ ለመሞት ቢቸኩልም መንጋውን እንዲሁ ሊበትን ግን አልወደደም።
ስለዚህም ወታደሮችን "እባካችሁ ሕዝቡን ልሰናበት አንድ ቀን ታገሱኝ።" አላቸው። ወታደሮቹ ከፊቱ የሚታየው ግርማው ደንቋቸው ነበርና ፈቀዱለት። ቅዱሱም ከሕይወቱ የቀረችውን ሃያ አራት ሰዓት ይጠቀምባት ዘንድ ምዕመናን ልጆቹን ሁሉ ጠራ።
ቅዳሴ ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ፈትቶ ለሁሉም አቀበላቸው። (በጊዜው የማይቆርብ ክርስቲያን አልነበረምና።)
ከቅዳሴ መልስም የተፈጠረውን ሁሉ ነግሮ ወደ ክርስቶስ ሊሔድ እንደ ናፈቀ ነገራቸው። ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ሲረዱ ፈጽመው አዘኑ። እርሱም በቀናችው እምነት እስከ ሞት ድረስ እንዲጸኑ አስተምሯቸው ከባልንጀራው ቅዱስ አላኒቆስ ጋር በወታደሮች እጅ ወደቀ።
እነርሱም ቅዱሳኑን ወስደው በመኮንኑ አርያኖስ ፊት ለፍርድ አቀረቧቸው። አርያኖስም የአባ አብሳዲ የፊቱ ግርማ ቢስበው ላለመግደል ወስኖ ሊያባብለው ወሰነ። "አንተ ክቡር ሰው ነህና ለንጉሡ ታዘዝ፤ ለጣዖትም እጠን።" አለው።
ቅዱስ አብሳዲ ግን "ክብሬ ክርስቶስ ነውና ፈጣሪዬን በምንም ነገር አልለውጠውም።" ሲል እቅጩን ነገረው። እንደማያሳምነው ሲረዳም ከአባ አላኒቆስ ጋር ያሰቃዩአቸው ዘንድ አዘዘ።
በምስክርነት አደባባይም በመንኮራኩር (አካልን የሚበጣጥስ ተሽከርካሪ ብረት ነው።) አበራዩአቸው። እግዚአብሔር ግን አዳናቸው። እንደ ገና እሳት አስነድደው እዚያ ውስጥ ጨመሯቸው። እሳቱም ግን ሊበላቸው አልቻለም።
በመጨረሻም መኮንኑ አንገታቸው ይሰየፍ ዘንድ አዘዘ። ከመሰየፋቸው በፊትም ቅዱሳኑ ጸሎትን አደረሱ። አባ አብሳዲ ነጭ የቅዳሴ ልብሱን ለብሶ ወደ ሰይፍ ቀረበ። ወታደሮች ደግሞ ሁለቱን ቅዱሳን እንደታዘዙት ሰየፏቸው። በክብርም ዐረፉ።
<3 አባ በግዑ ጻድቅ <3
እኒህ አባት በመካከለኛው ዘመን የሃገራችን ታሪክ ሰፊ ቦታን ይዘው ይገኛሉ። ተጋድሏቸውን የፈጸሙት በደብረ ሐይቅ ነው። ጻድቁ ብዙ ጊዜ የኋለኛው ዘመን ሙሴ ጸሊም ይባላሉ። ብዙ የሕይወታቸው ጐዳና ተመሳሳይ ነው።
ልክ ቅዱስ ሙሴ ጸሊም ከኃጢአት ከሽፍትነት ሕይወት እንደ መጣው ሁሉ አባ በግዑም አስቸጋሪ ሰው እንደ ነበሩ ይነገርላቸዋል። ከዚያ የከፋ የኃጢአት ኑሮ እግዚአብሔር ሲጠራቸው ግን ክሳደ ልቡናቸውን አላደነደኑም። "እሺ" ብለው ንስሐ ገቡ እንጂ።
ከዚያም በደብረ ሐይቅ (ወሎ) በፍጹም ተጋድሎ ኑረዋል። ያዩ ሁሉም ፍጹም ያደንቁ ነበር። ስትበላ ስትጠጣ የኖረችውን ሰውነት ራሳቸውን ውኃ ለዘመናት በመከልከል ቀጥተዋታል። ስለዚህም "ውኃ የማይጠጣው አባት" ይባሉም ነበር። ጻድቁ ሲያርፉ ፈጣሪያቸው አክብሯቸዋል።
አምላከ አበው ቅዱሳን አሠረ ፍኖታቸውን ይግለጽልን። ከበረከታቸውም ያድለን።
እንኳን ለቅድስት አንስጣስያ ሰማዕት እና ቅዱስ አቦሊ ጻድቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
እስኪ ዛሬ በጥቂቱ የተባረኩ (ቡሩካት) እናቶቻችን እንዘክር። "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል። እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቡርክት እምቡሩካን፣ ኅሪት እምኅሩያን" ናትና።
ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች። ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች። እርሷ እመ ብርሃን፣ የአምላክ እናቱ፣ የሰውነታችን መመኪያ ናትና።
እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት፣ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ" ማለታችን ነው።
፩."ንጽሕት" ትባላለች። ሌሎች ሰዎች (ቅዱሳን) ቢነጹ ከገቢር፣ ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም። እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከኃልዮ ንጽሕት ናት።
"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ።
(ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው፤ ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም።)" እንዲል።
(ተአምረ ማርያም)
፪."ጽንዕት" እንላታለን። ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው። እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና።
"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት።
(ቅዱስ ያሬድ)
ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም - ማርያም ዘላለማዊት ድንግል ናት።" እንዳለ።
(መጽሐፈ ቅዳሴ)
፫.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን። ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው። እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ - የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና።
፬.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን። ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል፣ እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና።
የእመ ብርሃን ይቆየንና ደግሞ ሌሎች ቅዱሳት እናቶቻችንን እንመልከት። እናቶቻችን ስናከብር የምንጀምረው በቅድስት ሔዋን ነው። ብዙ ጊዜ የእናታችን ሔዋን ጥፋቷ እንጂ በጐ ነገሯ፣ ደግነቷ፣ ንስሐዋ አይነገርላትም። ሆኖም እናታችን ቅድስት ሔዋን ክብር የሚገባት ሴት ናት።
ክርስቶስ ሰው የሆነ እርሷንና ልጆቿን ለመቀደስ ነውና። "ከመ ይስዓር መርገማ ለሔዋን ዲበ ዕፅ ተሰቅለ" እንዲል።
(ድጓ)
ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን እነ ሐይከል፣ እድና፣ ሣራ፣ ርብቃ፣ አስኔት፣ ሲፓራ፣ ሐና፣ ቤርሳቤህን የመሰሉ እናቶቻችን በበጐው መንገድ ፈጣሪን ደስ አሰኝተዋል። በዘመነ ሥጋዌም ቅዱሳቱ ሐና፣ ኤልሳቤጥ፣ ማርያም፣ ሶፍያ፣ ሰሎሜ፣ ዮሐና እና ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በጐነታቸው ያበራል።
ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለሁለት ሺህ ዓመታት የተነሱ አእላፍ ቅዱሳት እናቶቻችንን ግን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም። በቅድስናቸው አራዊትን ያሰገዱ፣ ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ፣ አጋንንትን የረገጡ፣ በዘንዶ ላይ የተጫሙ ብዙ እናቶችን ቤተ ክርስቲያን አፍርታለች።
ዛሬም ቢሆን በበርሃና በከተማ በጐውን ጐዳና የተከተሉ ብዙ እናቶች እንዳሉን እናውቃለን። አንድም እናምናለን። ግን በከተሞች የምንመለከተው ሥርዓቱን የለቀቀው የበርካታ እኅቶቻችን አካሔድ ለሃገርም ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ ስጋት ነው። ክብርና ነውር የማይለይበት ዘመን ይመስላል።
ይህንን እያነበባችሁ ያላችሁ እኅቶቼ! አንድ ነገር ልንገራችሁ። በመልካቸው ብዙዎችን ያጋጩ፣ አጊጠው በመታየታቸው ብዙዎችን ያሰናከሉ፣ ለብዙ ምዕመናንም የጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሴቶች በታሪክ ነበሩ።
የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ያሉት ከመሬት በታች ነው። አፈር በልቷቸዋል። ስም አጠራራቸውም ጠፍቷል። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ዛሬ በዘላለማዊው እሳት እየተቃጠሉ በሲኦል በጥልቁ ውስጥ አሉ።
እናም ወገኖቼ! ይህን አውቀን እንንቃ። ይህ ዓለም ጠፊም አጥፊም ነውና። እድሜአችን ቢረዝምና ከዚህ በኋላ ለመቶ ዓመታት ብንኖርም እርሱም ማለቁ አይቀርምና። ምርጫችን ዘላለማዊው ሕይወት ይሁን ትላለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን።
እንኳን ለአምስቱ ቅዱሳን መቃብያን እና ቅዱስ ዮሐንስ ከማ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 አምስቱ መቃብያን <3
እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው። አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ነቢይና ካህን አድርጐ ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው።
አባታችን አዳም ግን ስህተት አግኝቶት ከገነት ወጣ። መከራና ፍዳም አገኘው። በኋላም ለመቶ ዓመታት አልቅሶ ንስሐ ገባ። ጌታም ንስሐውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው።
ስለዚህም ምክንያት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ትንቢት ሲነገር፣ ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር፣ ምሳሌም ሲመሰል ኖረ። ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ።
ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ። በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም። ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ።
ከእርሱም ይስሐቅ ከዚያም ያዕቆብ ደጋጉ ተገኙ። ያዕቆብም "እስራኤል" ተብሎ በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ። በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ረሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው።
በዚያም ለሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ። እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እስራኤልን አሰባቸው። የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው።
ይኸውም በጸናች እጅ በበረታችም ክንድ፣ በዘጠኝ መቅሰፍት፣ በአሥረኛ ሞተ በኩር፣ በአሥራ አንደኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው። በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው። ከዚህ ዘመን ጀምሮም እስራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ።
አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና አሮን በክህነት መሯቸው። ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ በአሮን አልዓዛር ተተኩ።
ከዚህ በኋላ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል መሳፍንት እየተቀያየሩ አስተዳደሯቸው። ሲበድሉ ጠላት እየገዛቸው ሲጸጸቱ በጐ መስፍን እየመጣላቸው ከነቢዩ ሳሙኤል ደረሱ።
በዚህ ጊዜም ሕዝቡ እንደ አሕዛብ ሥርዓት ንጉሥ በመፈለጋቸው ክፉው ሳዖል ለአርባ ዓመት ገዛቸው። ቀጥሎ ግን እንደ አምላክ ልብ የሆነ ቅዱስ ሰው ዳዊት ነግሦላቸው እስራኤል ከፍ ከፍ አሉ። ከቅዱስ ዳዊት እስከ ሮብዓም ቆይተው ግን እስራኤል ከሁለት ተከፈሉ።
አሥሩ ነገድ በሰማርያ ሲኖሩ ግፍን ስላበዙ ስልምናሶር ማርኮ አሦር አወረዳቸው። ባሮችም አደረጋቸው። ሁለቱ ነገድ ደግሞ ከብረው ገነው በኢየሩሳሌም ቢኖሩም እነርሱም አመጸኞች ነበሩና ናቡከደነጾር ወስዶ የባቢሎን ባሪያ አደረጋቸው።
እግዚአብሔር ግን እንደ ነቢያቱ ቃል ሰባው ዘመን ሲፈጸም በኃይል ወደ ርስታቸው መለሳቸው። በዚያም ዘሩባቤል የሚባል ደግ ንጉሥ ነግሦላቸው ቤተ መቅደስ ታንጾላቸው ኖሩ። ክፋታቸው ግን ማብቂያ አልነበረውምና ከዘሩባቤል በኋላ ቅን ንጉሥን ማግኘት አልቻሉም።
እግዚአብሔር ግን ምሕረቱንና መግቦቱን አይተውምና አልዓዛርን የመሰሉ ደጋግ ካህናትን እያስነሳ ሰው እስከሚሆንባት ቀን ድረስ አቆይቷቸዋል። በዚህም ምክንያት ይህ ዘመን "ዘመነ ካህናት" ተብሏል።
በዚህ በዘመነ ካህናት ውስጥ ደግሞ በጐነታቸው የታወቀላቸው ግን ደግሞ መከራው የበዛባቸው እስራኤላውያን ነበሩ። ብዙ ጊዜ የሚጠሩት "መቃብያን" በሚል ስም ነው።
በያዕቆብ እስራኤል፣ በዔቦር ዕብራውያን፣ በይሁዳ አይሁድ፣ በፋሬስ ፈሪሳውያን፣ በሳዶቅ ሰዱቃውያን እንደተባሉት ሁሉ እነዚህም በአባታቸው በመቃቢስ ምክንያት መቃብያን ተብለዋል። ታሪካቸው ሰፊና በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈ ሲሆን እኛ ግን በአጭሩ አንዷን የታሪክ ዘለላ ብቻ እንመለከታለን።
በዘመኑ መቃቢስ የሚባል ደግ ሰው አምስት ወንዶች ልጆችን (መቃብያንን) ወልዶ ነበር። እነዚህም በመልክ ይህ ቀራችሁ የማይባሉ በጠባይ እጅግ የተመሰገኑ በኃይላቸው ጽናትም የተፈሩ ነበሩ።
በተለይ ሦስቱ ከግሩማን አራዊት አንበሳና ድብ ታግለው ያሸነፉ በጦርነትም ጠላትን ያንበረከኩ ነበሩ። ታዲያ ይህ ሁሉ የተሰጣቸው ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና ፈጣሪያቸውን በንጹሕ ልብ ያመልኩት ነበር።
በዘመኑ ደግሞ ሞዐባውያንና ሜዶናውያን አካባቢውን ያስገብሩ ነበር። በተለይ የሞዐቡ ንጉሥ ጺሩጻይዳን ከክፋቱ ብዛት ሰባ ጣዖታት በወንድና በሴት ምሳሌ አስቀርጾ ያመልክ ነበር። ከዚያም አልፎ ሕዝቡን "አምልኩ" እያለ ያውክ፣ ይቀጣ፣ ይገድልም ነበር።
ቅዱሳን መቃብያን ይህንን ሲሰሙ ወደ እርሱ ገሰገሱ። ምንም እንኳ ሊያጠፉት ኃይል ቢኖራቸውም አላደረጉትም። ይልቁኑ ቀርበው ዘለፉት እንጂ።
እርሱም "ጣዖትን አናመልክም።" ስላሉ ለአንበሳ ጣላቸው። አንበሶቹም ለቅዱሳኑ ሰግደው የንጉሡን ወታደሮች ፈጇቸው። እርሱም ሦስቱን ወደ እሥር ቤት ጣላቸው። በዚህ ጊዜ ሁለቱ ወንድሞቻቸው መጥተው ተቀላቀሉ።
ቀጥሎም አምስቱንም አስወጥቶ በሰይፍ አስመታቸው። ከተገደሉ በኋላም ወደ ውኃ ጥሏቸው በእሳት አቃጥሏቸው ነበር። ባይሳካለት ስለ ተቆጣ ሳይቀበሩ እንዲጣሉ አዘዘ። ከአሥራ አራት ቀናት በኋላም የቅዱሳኑ አካል እንደ መብረቅ እያብለጨለጨ ተገኝቶ በክብር እንዲቀበር ሆኗል።
ቀሪው ታሪካቸው በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈ አይደለምን!
<3 ቅዱስ አግናጥዮስ <3
ይህ ቅዱስ ሰው ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የጠገበ በመሆኑ በመላው ዓለም ዝነኛ ነው።
እርሱ፦
በክርስቶስ እጅ ተባርኳል፣
ፈጣሪውን ፊት ለፊት አይቷል፣
ሐዋርያትን አገልግሏል፣
ከምሥጢር አባት ከዮሐንስ ወንጌላዊ እግር ተምሯል፣
ስለ ክርስትና ለአንበሶች ተጥሎ በመገደሉ "ምጥው ለአንበሳ" ይባላል።
ቅዱስ አግናጥዮስ የተወለደው በክርስቶስ አምላካችን መዋዕለ ስብከት (በ፴ ዓ/ም አካባቢ) እንደ ሆነ ይታመናል። በትውፊትም በማቴ. ፲፰፥፩ ላይ ያለው ሕፃን እርሱ ነው ይባላል።
ሐዋርያት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ሲጠይቁት አንድ ሕፃንን (አግናጥዮስን) ከመሃል አቁሞ "ካልተመለሳችሁ እንደዚህም ሕፃን ካልሆናችሁ ከቶውንም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም።" ብሏቸዋል።
ከጌታ ዕርገት በኋላም ሐዋርያት ለወንጌል ሲፋጠኑ ሕፃኑ ቅዱስ አግናጥዮስ እየተከተለ አገልግሏል፤ ተምሯል። ኢየሩሳሌም በጥጦስ አስባስያኖስ ቄሣር በጠፋችበት ዓመት (በ፸ ዓ/ም) ቅዱሱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሹሟል።
ከዚህ በኋላም ለሁለት እና ሦስት አሥርት ዓመታት ከወንጌላዊ ዮሐንስ ጋር አብሮ ወንጌልን ሰብኳል። የዚህ ቅዱስ ተጋድሎ ጫፍ የደረሰው ከ፻ ዓ/ም በኋላ ሁሉም ሐዋርያት ሰማዕት በመሆናቸውና ትልቁን ኃላፊነት እርሱ በመሸከሙ ነው። የወቅቷን ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳኑ ቀሌምንጦስ ዘሮምና ፖሊካርፐስ ዘሰርምኔስ ጋር ሆኖ እስከ ደም ጠብታ ጠብቋል።
ከዚህ በኋላ ቅዱስ አግናጥዮስ ለዘመናት ወንጌልን እየሰበከ በሕይወቱና በትምህርቱ አስተማረ። ብዙ መልእክቶችን (ድርሳናትንም) ጻፈ። በመጨረሻው ግን በጠራብሎስ ቄሣር ተይዞ በብረት ሰንሰለት ታስሮ ከአንጾኪያ (ሶርያ) ወደ ሮም (ጣልያን) ተወሰደ።
ደሙ እስኪፈስም ገረፉት። ዛሬ በሮም ከተማ ግማሽ አካሉ ፈርሶ በሚታየው ስታዲየም (በአባቶቻችን አጠራር ተያጥሮን) እንዲገደል ተወሰነበት። በወቅቱ ባደረገው ንግግርም ቄሣሩና ሕዝቡ ድፍረቱን አደነቁ። በመጨረሻም ለአንበሳ እንዲሰጥ ተደርጐ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነ።
<3 ቅድስት አስቴር <3
ይህቺ ቅድስት እናት፦
እስራኤል በባቢሎን ምርኮ ሳሉ የነበረች፣
አባቷ አሚናዳብ ባለ መኖሩ በአጐቷ መርዶክዮስ እጅ ያደገች፣
እጅግ ውብ በመሆኗ የአርጤክስስ ሚስት (ንግሥት) ለመሆን የበቃች፣
ራሷን መስዋዕት አድርጋ ወገኖቿን አይሁድን ከሞት ያተረፈች፣
ለመርዶክዮስ ክብርን ለአማሌቃዊው ሐማ ደግሞ ስቅላትን ያስፈረደች እና እግዚአብሔር ሞገስ የሆናት እናት ናት።
ዛሬ ዕረፍቷ ነው።
አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን ባጸናበት ቅዱስ መንፈሱ እኛንም ያጽናን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።
ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪.ቅዱሳን ጸጋ ዘአብና እግዚእ ኃረያ
፫.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያ
፬.ቅድስት አስቴር
፭.አባ ፊሎንጐስ ሊቀ ጳጳሳት
፮.አባ ጳውሊ ጻድቅ
፯.ጻድቃን ቅዱሳን ዘከዲህ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፪.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
፫.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤጲስቆጶስ)
፬.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፭.ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል)
፮.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮጵያዊ)
፯.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
"ንግሥቲቱም አስቴር መልሳ፦ 'ንጉሥ ሆይ! በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ ንጉሡንም ደስ ቢያሰኘው ሕይወቴ በልመናዬ ሕዝቤም በመሻቴ ይሰጠኝ። እኔና ሕዝቤ ለመጥፋትና ለመገደል ለመደምሰስም ተሸጠናልና።' "
(አስቴር ፯፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
"አባቴ ጊዮርጊስ ሆይ! የልቤን ኀዘን ስነግርህ ፈጥነህ ጸሎቴን ስማኝ፤ ነገሬንም አድምጠኝ።
ያዘኑትን የምታረጋጋ ሆይ ወደ እኔ ቅረብ፤ በአጠገቤም ተገኝተህ አለሁልህ በለኝ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
እንኳን ለጻድቅ የዋሕና ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ <3
ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ "እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ፤ አይጸጸትም።"
(መዝ. ፻፴፩፥፲፩)
አሁን በእግዚአብሔር መጸጸት ኑሮበት አይደለም። ቅዱስ ዳዊት የማያጸጽት ፍጹም ወዳጅ መሆኑን ሲገልጥ ነው እንጂ። ጌታ ቅዱስ ዳዊትን "እንደ ልቤ የሆነ፣ ፈቃዴን የሚፈጽም፣ ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት።" (መዝ. ፹፰፥፳) ብሎ ሲናገር ሰምተን እጅግ አደነቅን።
እንደ አምላክ ልብ ሆኖ መገኘት ምን ይረቅ?! ምንስ ይደንቅ?! ለዚህ አንክሮ ይገባል!
ጌታ ይቀጥልና ደግሞ "ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ።" (መዝ. ፹፰፥፴፭) ይላል።
አቤት አባታችን ዳዊት ክብር፣ የክብር ክብር፣ ውዳሴና ስግደትም ላንተ በጸጋ ይገባል እንላለን።
ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት ሰባት ሃብታት ሲኖሩት፦
፩.ሃብተ ትንቢት
፪.ሃብተ መንግሥት
፫.ሃብተ ክህነት
፬.ሃብተ በገና (መዝሙር)
፭.ሃብተ ፈውስ
፮.ሃብተ መዊዕ (ድል መንሳት) እና
፯.ሃብተ ኃይል ተብለው ይታወቃሉ።
በሰባቱ ስሞቹም፦
፩.ጻድቅ
፪.የዋህ
፫.ንጹሕ
፬.ብእሴ እግዚአብሔር
፭.ነቢየ ጽድቅ
፮.መዘምር እና
፯.ልበ አምላክ ተብሎ ይጠራል።
<3 ልደት <3
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ስለ ልደቱ ሲናገር "እስመ ናሁ በኃጢአት ተጸነስኩ - በኃጢአት ተጸነስኩ።" ይላል።
(መዝ. ፶፥፭)
አበው እንደ ነገሩን የቅዱስ ዳዊት አባት ደጉ እሴይ ከነገደ ይሁዳ የኢዮቤድ ልጅ ነው።
ሚስቱን ሁብሊን አንድ ጐልማሳ በዝሙት ዓይን ሲፈልጋት ተመልክቶ ነበር። አንድ ቀንም መንገድ ሔድኩ ብሎ ግን ያንን ጐልማሳ መስሎ ተመልሶ አብሯት አድሯል። በዚያች ሌሊትም ቅዱስ ዳዊት ተጸንሷልና እንዲህ ብሏል።
<3 ዕድገት <3
ቅዱስ ዳዊት ከሕፃንነቱ ጀምሮ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ነበር። ሕፃን ሳለ በእረኝነት በጐቹን አያስነካም ነበር። አንበሳውን በጡጫ፣ ድቡን በእርግጫ፣ ነብሩን በሩጫ የያዙትን ያስጥላቸው ነበር። በጥቂቱ በበግ እረኝነት ስለ ታመነ ለእስራኤል እረኛ ሊሆን ተመርጧል።
<3 መቀባት <3
እግዚአብሔር ሳዖልን ከናቀው በኋላ ከእሴይ ልጆች መካከል "እንደ ልቤ የሆነውን ቀብተህ አንግስልኝ።" ቢለው ነቢዩ ሳሙኤል ቤተ ልሔም ገብቷል።
በዚያም ከኤልያብ እስከ አሚናዳብ ሰባቱን የእሴይን ልጆች ቢፈትን አልሆነም። በቅዱስ ሚካኤል ጠቋሚነት ግን ከእረኝነቱ ዳዊት ተጠራ። ገና ከርቀት ሲመጣ የዘይት ቀርኑ ቦግ ብሎ ተከፈተ። በቅዱስ ዳዊት ራስ ላይም እንደ እሳት ፈላ። በአምላክ ምርጫም በአሥራ ሁለት ዓመቱ ንጉሥ ተባለ።
<3 ዳዊትና ጐልያድ <3
ኢሎፍላውያን በጠላትነት በተነሱባቸው ጊዜም ጐልያድ የሚሉት የጌት ሰው እስራኤልን ሲያስጨንቅ ለአርባ ቀናት ቆይቶ ነበር። ለአምላኩ ስምና ክብር የሚቀና ቅዱስ ዳዊት ግን በድፍረት ገጥሞ በፈጣሪው ኃይል በጠጠር ጥሎታል። ከእስራኤልም ሽሙጥን አርቋል። ግን ቅዱሱ ብላቴና፣ ጐልያድ ደግሞ ስድስት ክንድ (ሦስት ሜትር) የሚረዝም ሰው ነበር።
<3 ስደት <3
ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቶ ዙፋን አልጠበቀውም። ጠላታቸውን ጥሎ ስላዳናቸው ፈንታ ሳዖልን በገና እየደረደረ ስለ ፈወሰው ፈንታም ሊገደል ተፈለገ። ፈጣሪው ከእርሱ ጋር ባይሆንም ይገድሉት ነበር።
እርሱ ግን ለአሥራ ስምንት ዓመታት በትእግስት ተሰደደ። ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ጠላቱን ሳዖልን አሳቻ ሥፍራ ላይ አግኝቶ በምሕረት ተወው። በዚህ የዋሕነቱም በብሉይ ሆኖ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ።" የምትለውን ሕግ ፈጸማት።
(ማቴ. ፯፥፵፭ ፣ መዝ. ፲፮፥፬)
<3 ንግሥና <3
ቅዱስ ዳዊት የስደት ዘመኑ ሲፈጸም ሳዖል ሞተ። ምን ጠላቱ ቢሆን "የሳዖል ገዳይ ነኝ።" ያለውን ተበቀለ። ስለ ጠላቱም አለቀሰ። ሠላሳ ዓመት ሲሆነው ነግሦ ለሰባት ዓመታት በኬብሮን ለሠላሳ ሦስት ዓመታት በኢየሩሳሌም (ጽዮን) ሕዝበ እግዚአብሔርን ጠብቋል።
በዘመኑም ጠላቶቹን ሁሉ ድል አድርጓል። በልጁ አቤሴሎም እጅ መሰደድን በሳሚ ወልደ ጌራ መሰደብንም ታግሷል።
<3 ንስሐ <3
ቅዱሱ ንጉሥ ሁሉ ነገር የተሰጠው አባት ነው። ሁሉ ሕይወቱም ለእኛ ትምህርት ቤት ነው። ሰው ነውና የኦርዮን ሚስት ቀምቶ ኦርዮን አስገድሎ ነበር። ጉዳዩን ነቢዩ ናታን በምሳሌ ሲነግረው ፍጹም ተጸጸተ።
ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ አለቀሰ። መሬትንም በእንባው ክንድ አራሳት። ሐረግ እስከ ማብቀልም ደረሰ። እግዚአብሔርም ንስሐውን ተቀብሎ ከፍ ከፍ አደረገው። በንስሐ ለምትገኝ ጸጋም ምሳሌ ሆነ።
<3 ነቢይነት <3
በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቅዱስ ዳዊትን የሚያህል ነቢይ (ምሥጢር የበዛለት) አልተገኘም። "ከዓለም በፊት እንዲህ ነበረ።" ብሎ ከዚያ ከስነ ፍጥረት እስከ ዳግም ምጽዓት የተናገረ እርሱ ነው።
ስለ መላእክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ደናግልና መነኮሳት ሁሉ መናገሩ ይደነቃል። ስለ ድንግል ማርያምና ስለ መድኃኒታችን ክርስቶስም አምልቶ አስፍቶ ተናግሯል። መቶ ሃምሳ ምዕራፎች ባሉት መጽሐፈ ትንቢቱ ኃላፍያትንና መጻዕያትን ተመልክቷል።
ስለዚህም አበው፦
"አልቦ ምሥጢር ወአልቦ ትንቢት
ዘኢተናገረ አቡነ ዳዊት።" ይላሉ።
<3 መዝሙር <3
ቅዱሱ ነቢይና ንጉሥ በጣም የሚታወቀው በዝማሬው ነው። ለራሱ ባለ አሥር አውታር ለመዘምራኑ ደግሞ ባለ ስምንት አውታር በገናን አዘጋጅቶ ፈጣሪውን ያመሰግን ነበር። ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ስብሐተ እግዚአብሔር እንዳይቋረጥ ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት መዘምራንን በአሳፍ መሪነት መድቦ ነበር።
ራሱም በፍጹም ተመስጦ ማር ማር እያለው እግዚአብሔርን ያመሰግነው ነበር። "ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው።" እንዲል።
(መዝ. ፻፲፰፥፻፫)
የዳዊት መዝሙሩ ለአጋንንት ትልቅ ጠላት ነው። ቅዱሳን መላእክትም በዳዊት መዝሙር ይዘምራሉ።
"በዘቦቱ ይሴብሑ ሰማያውያን ወምድራውያን" እንዲል።