††† እንኳን ለካህኑ ሰማዕት አባ ኦሪ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ አባ ኦሪ ቀሲስ †††
††† ይህ ቅዱስ አባት የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ነው:: በዘመኑ (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) ክርስቲያን መሆን ብቻውን ለሞት እንደሚያበቃ ወንጀል ይቆጠር ነበር:: በጊዜው ክርስቲያን ከመሆን በባሰ መንገድ እረኛ ካህን ሆኖ መገኘት በጣም ከባድ ነበር::
ከመነሻውም ያን ጊዜ ክህነት የሚሰጠው በሕዝቡና በሊቀ ጳጳሱ ምርጫ ነበር እንጂ እንደ ዘንድሮ "እኔን ሹሙኝ" ማለት ልማድ አልነበረም:: ምዕመናንም እረኛቸውን ሲመርጡ በጉቦ: በዝምድና አይደለም:: በርትቶ የሚያበረታቸውን: ለመንጋው ራሱን አሳልፎ የሚሰጠውን ይመርጣሉ እንጂ::
ያልሆነ ሰው ለክህነት ቢመረጥ አንድም ክዶ ያስክዳል: ሲቀጥልም ለሕዝቡ መሰናክል መሆኑ አይቀርም:: በጊዜው (በዘመነ ሰማዕታት) የነበሩ ካህናት የቤት ሥራቸውም ማስተማር ብቻ አልነበረም:: በድፍረት በምዕመናን ፊት አንገታቸውን ለሰይፍ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር እንጂ::
ይህንን በገሃድ መፈጸም ከቻሉ አበው አንዱ ደግሞ አባ ኦሪ ቀሲስ ናቸው:: ቅዱሱ ተወልደው ባደጉባት ሃገረ ስጥኑፍ (የግብፅ አውራጃ ናት) መጻሕፍትን የተማሩ: ተወዳጅ እና ደግ ሰው ነበሩ::
አባ ኦሪ ገና ከወጣትነት ቀዳሚ ግብራቸው መንኖ ጥሪት (ምናኔ) ነበር:: በንጽሕናቸው ደስ የተሰኙ ምዕመናንም "ቅስና ተሹመህ ምራን: አስተምረን::" ቢሏቸው አበው ውዳሴ ከንቱን አይፈልጉምና "አይሆንም" አሉ::
ነገሩ ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረና አባ ኦሪ ቅስናን ተሹመው ያገለግሉ ገቡ:: ሕዝቡን በማስተማር: በመምከር: ደካማውን በማጽናት ብዙ ደክመዋል::
ከቅድስናቸው የተነሳ ቅዳሴ ሊቀድሱ ሲገቡ ጌታችን በገሃድ ይገለጥላቸው ነበር:: ሠራዊተ መላእክትም ከበው ይነጋገሯቸው ነበር::
ሥጋውን ደሙን በማቀበልም ተግተው ዘመናት አለፉ:: ቆይቶ ግን ያ በዜና ይሰሙት የነበረ መከራ (ሰማዕትነት) በደጃቸው ደረሰ:: በጊዜው ብዙ ሰው በሰማዕትነት አለፈ:: አባ ኦሪም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ገብተው ስለ ራሳቸውና ሕዝቡ ጽናትን: ደኅንነትን ለመኑና ከቤተ ክርስቲያን ወጡ::
በቀጥታ የሔዱትም ወደ ዐውደ ስምዕ (የምሥክርነት አደባባይ) ነበር:: በመኮንኑ ፊት ቀርበው "ክርስቶስ አምላክ: ፈጣሪ: የሁሉ ጌታ ነው:: የእናንተ ጣዖት ግን ጠፊ: ረጋፊ: ወርቅ: ብር: እንጨትና ድንጋይ ነው::" ሲሉ በድፍረት ተናገሩ::
መኮንኑም ከአነጋገራቸው የተነሳ ተቆጥቶ ሥቃይን አዘዘባቸው:: ወታደሮቹ ይሆናል ያሉትን ማሰቃያ ሁሉ አባ ኦሪ ላይ ሞከሩ:: በኋላም ወደ ጨለማ እሥር ቤት ወስደው ጣሏቸው:: በእሥር ቤት ውስጥም ድውያንን ፈወሱ: ተአምራትን ሠሩ::
ይሕንን ዜና የሰሙ አሕዛብ ብዙ ድውያንን ሰብስበው መጡ:: ቅዱሱም ሁሉን በጸሎታቸው ፈወሱ:: በዚህ ምክንያትም ብዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና መጥተዋል:: በክርስቶስ አምነውም ለክብር በቅተዋል::
ቅዱሱንም ከእሥር ቤት አውጥተው ብዙ ካሰቃዩዋቸው በኋላ በዚህች ቀን ገድለዋቸው ሰማዕትነትን አግኝተዋል:: በአክሊለ ጽድቅ ላይ አክሊለ ካህናትን: በአክሊለ ካህናትም ላይ አክሊለ ሰማዕታትን ደርበዋል::
††† አምላከ ቅዱሳን በአባቶቻችን ጽናት ያጽናን:: ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን::
††† ነሐሴ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ኦሪ ቀሲስ (ሰማዕት)
2.አባ ጲላጦስ ሊቀ ጳጳሳት
††† ወርኀዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
3.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)
††† "ስለዚሕ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና::" †††
(፩ቆሮ. ፲፥፲፬-፲፰)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለካህኑ ሰማዕት ቅዱስ አልዓዛር እና ለቅዱሳን ቤተሰቡ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ አልዓዛር ካህን †††
††† ይህ ቅዱስ #የብሉይ_ኪዳን_ሰማዕታትተብለው ከሚታወቁት ዋነኛው ነው:: የነበረበት ዘመንም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን " #ዓመተ_መቃብያን/ #ዘመነ_ካህናት" ይባላል::
በወቅቱ ሰሎሜ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ይኖር የነበረው ቅዱስ አልዓዛር በኢየሩሳሌም ተወዳጅ ነበር:: ሐረገ ትውልዱ ከአሮን ወገን ነውና በክህነቱ ተግቶ ያገለግል ነበር:: በዚያ ላይ ሊቀ ካህንነትን በመመረጡ ሕዝቡን ይሠራ: ያስተምር: ያስተዳድር ነበር::
ቅዱስ አልዓዛር ከተባረከች ሚስቱ ሰሎሜ 7 ወንዶች ልጆችን አፍርቷል:: እነርሱንም በሥርዓት አሳድጐ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጐ ነበር:: በዚያው ዘመን በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚኖሩ 3 እኩያን (ክፉ) ካህናት ነበሩ::
እነዚሁም ሕዝቡን ከማስቸገር: ፈጣሪን ከማሳዘን ቦዝነው አያውቁም ነበር:: የክፋታቸው መጨረሻ ግን የገዛ ሃገራቸውን ማጥፋት ሆነ:: ነገሩ እንዲህ ነው:- 3ቱም ተመካክረው የአልዓዛርን የሊቀ ካህንነት ቦታ ሊቀሙ ወስነው ወደ እርሱ ሔዱና እንዲህ አሉት::
"ሹመት በተርታ: ሥጋ በገበታ" ሲሆን ያምራልና እኛ በተራችን በወንበሩ ላይ እንቀመጥ::"
እርሱ ግን "ሕዝቡን ጠይቃችሁ ተሾሙ" አላቸው:: እነርሱም ሕዝቡን ጠርተው "ሹመት ይገባናል" ቢሏቸው ሕዝቡ መልሶ "አልዓዛርን የሾመው እግዚአብሔር ነውና እናንተም ከፈጣሪ ጠይቃችሁ ተሾሙ" አሏቸው::
በዚህ ጊዜ 3ቱ እኩያን ተቆጡ:: ምክንያቱም እግዚአብሔር እንደ ማይሰጣቸው ያውቃሉና:: ወዲያው ግን 3ቱም ከአካባቢው ጠፉ:: ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ጨካኙ የግሪክ ንጉሥ አንጥያኮስ ሔዱ::
አንጥያኮስ ማለት "ቀኝ ዐይናችሁን ገብሩልኝ" የሚል ንጉሥ ነው:: እርሱን " #ኢየሩሳሌም ባለቤት የላትምና ሒደህ ውረራት" አሉት:: "አጥሩ ጥብቅ ነው:: በምን እገባለሁ?" ቢላቸው "እኛ በመላ እናስገባሃለን" አሉት:: እርሱም 240,000 ሠራዊት አስከትቶ ወረደ::
እነርሱ ቀድመው ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ያስወሩ ጀመር:: "እናንተ ሹመት ብትነሱንም እኛ ግን አንጥያኮስን ያህል ንጉሥ በእሥራኤል አምላክ አሳምነን መጣን" እያሉ ይሰብኩ ገቡ:: ቅዱስ አልዓዛር "አትስሟቸው:: በዚያም ላይ አሕዛብ የተቀደሰውን ምድር መርገጥ የለባቸውም" ብሎ ነበር::
ነገር ግን አንዳንድ ችኩሎች አይጠፉምና ፈጥነው የከተማዋን በር ከፈቱት:: ሠራዊቱን ደብቆ ትንሽ ራሱን የቆመ የመሰለው አንጥያኮስ በምክንያት: በክፋትና በመላ ሁሉን ሠራዊቱን አስገባ:: የሚገርመው በጊዜው የከተማዋ ሕዝብ 12 እልፍ (120,000) ሲሆን ንጉሡ ያስገባው ሠራዊት ግን 24 እልፍ (240,000) ሆኖ ተገኘ::
ወዲያው አንጥያኮስ ሕዝቡን ሰበሰበና አልዓዛርን ለብቻው ጠርቶ ተናገረው:: "አንተ አምላክህን እንደምትወድ ሰምቻለሁ:: አንተ የበጉን መስዋዕት በልተህ: #ለስዕለ_ኪሩብ ሰግደህ: ሕዝቡን ግን እሪያ (አሳማ) እንዲበላና ለጸፀሐይ እንዲሰግድ አድርግልኝ" አለው::
ቅዱስ አልዓዛር መለሰለት:- "እግዚአብሔር የሾመኝኮ በጐ ሃይማኖትን ላስተምር እንጂ ለክፋት አይደለም:: ለሕዝቤ የክፋት አብነት ፈጽሞ አልሆንም" አለው:: ያን ጊዜ ንጉሡ በቅዱሱ ላይ ተቆጣ:: "የምልህን ካላደረግህ ብዙ ግፍ ይደርስብሃል" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የፈለግኸውን አድርግ" አለው::
በዚያን ጊዜ ንጉሡ የቅዱሱን ሚስትና 7 ልጆች እንዲያመጡለት አዘዘ:: ቅዱሱ እያየ ከፊቱ ላይ 7ቱንም ልጆቹን በሰይፍ አስመታቸውና 7ቱም ወደቁ:: ለአንድ አባት ይህ የመጨረሻው መራራ ፈተና ነው:: #አልዓዛር ግን ምን አንጀቱ በኀዘን ቢቃጠልም ከልጆቹ ለእግዚአብሔር አድልቷልና ቻለው ታገሠው::
በዚህ ለውጥ እንዳልመጣ ያየው ንጉሡ ሌላ ፍርድ ተናገረ:: ቅዱሱንና ሚስቱን ( #ሰሎሜን) በፈትል ጠቅልለው በሠም ነከሯቸው:: (ጧፍ እንደሚሠራበት መንገድ ማለት ነው:: )
አሁንም ግን ከአምልኮታቸው ፈቀቅ ባለማለታቸው ትልቅ ብረት ምጣድ ተጥዶ: 2ቱም ከነነፍሳቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ:: ቀጥሎም ሕዝቡን እንዲፈጁ አዋጅ ወጣ:: በከተማዋ ከነበረው ሕዝብ 40,000 ያህሉ ተገደሉ::
40,000 ያህሉ ሲማረኩ 40,000 ያህሉን ደግሞ #ይሁዳ የሚባል አርበኛ በር ሰብሮ ይዟቸው ሸሸ:: "እንሾማለን: እንሸለማለን" ብለው ሕዝባቸውን ያስፈጁ እነዚያ ካህናትም #እግዚአብሔር ፈርዶባቸው እነርሱም ተገደሉ:: ቅዱሱ የአልዓዛር ቤተሰብ ግን የክብርን አክሊል አግኝተዋል::
††† #የእሥራኤል_አምላክ ቸሩ እግዚአብሔር እንዲህ ካለው መከራ በኪነ ጥበቡ ይሰውረን:: ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን::
††† ነሐሴ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አልዓዛር ካህን (ሰማዕት)
2.ቅድስት ሰሎሜ ሰማዕት (ሚስቱ)
3."7ቱ" ቅዱሳን ሰማዕታት (ልጆቹ)
4.ቅዱስ አሞን ሰማዕት
††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
††† "አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ::
የቅድስናህንም #መቅደስ አረከሱ::
#ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት::
የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ::
የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት::
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውሃ አፈሰሱ::
የሚቀብራቸውም አጡ::" †††
(መዝ. 78:1)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቁጽረታ (ጽንሰታ) ለማርያም †††
††† ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል::
ስለ ምን ነው ቢሉ:-
ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ::
"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ::"
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው::"
(መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9, መኃ. 4)
ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል::
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ(አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::
ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::
የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::
ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ: በማኅጸኗ ስትደርስ አየ::
እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::
በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::
እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ::
(ቅዳሴ ማርያም)
††† ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት †††
††† ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ ናት:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በዚህች ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልጶስ ይዟቸው ሔደ:: በዚያም ጌታ ከእነሱ ራቅ ብሎ ተቀምጦ ነበርና የማይሰማቸው መስሏቸው እርስ በእርስ ይከራከሩ ገቡ::
የክርክራቸው መነሻ ደግሞ ጌታችን ነበር:: የዋሃን (ገና ምሥጢርን ያልተረዱ) ነበሩና አንዱ ተነስቶ "ኤልያስ ነው": ሌላኛው "ሙሴ": ሦስተኛው "ኤርምያስ ነው" በሚል ተከራከሩ:: ቅዱስ ጴጥሮስ ለብቻው ቆሞ ነበርና ጠርተው "ሃሳባችንን አስታርቅልን:: ለአንተስ ማን ይመስልሃል?" አሉት::
አረጋዊው ሐዋርያም ተቆጣቸው:: "እናንተ እንደምታስቡት እርሱ ከነቢያት አንዱ ሳይሆን "እግዚአ ነቢያት-የነቢያት ፈጣሪ ነው" አላቸው:: ወዲያውም ጌታ ጠርቷቸው ወደ እርሱ ቀረቡ::
ቸር አምላክ "ለምን ተጠራጠራችሁኝ" ብሎ መገሰጽ ሲችል እንዳይደነግጡ ጥያቄውን በፈሊጥ አደረገ:: "የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?" አላቸው:: እነርሱም በልባቸው ያለውን የሌላ አስመስለው ተናገሩ::
ጌታችን "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ጸጥ አሉ:: ገና ሃይማኖታቸው አልጸናም ነበርና:: በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነስቶ "አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው-አንተ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ ነህ" አለው:: (ማቴ. 16:16)
ይህች ቃል የክርስትና ሃይማኖት መሠረት ናትና ጌታችን "አንተ ዓለት (መሠረት) ነህ" ብሎ የቤተ ክርስቲያንን በዚህ እምነት ላይ መመስረት ተናገረ:: ለቅዱስ ጴጥሮስም "መራሑተ መንግስት-የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ (ሥልጣን)" ተሰጠው::
††† ሊቀ ሐዋርያትነትንም ደረበ:: ዛሬ ለበርካቶቹ የጸነነባቸው ይሔው እምነት ነው::
ኢየሱስ ክርስቶስን "አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ ማርያም:
አካላዊ ቃል:
ሥግው ቃል:
ገባሬ ኩሉ:
የሁሉ ፈጣሪ"ብለው ካላመኑ እንኳን ጽድቅ ክርስትናም የለም::
††† አፄ ናዖድ ጻድቅ †††
††† ሃገራችን ኢትዮጵያ ምስፍና ከክህነት: ንግሥናን ከጽድቅ ያጣመሩ ብዙ መሪዎች ነበሯት:: ከእነዚህ አንዱ ደግሞ አፄ ናዖድ ናቸው:: ጻድቁ ንጉሥ የነገሡት ከ1487 እስከ 1499 ዓ/ም ሲሆን ለእመቤታችን በነበራቸው ልዩ ፍቅር ይታወቃሉ:: ካህን እንደ ነበሩም ይነገራል::
ዛሬ ሁላችን የምንወዳትን ጸሎት (ሰላም ለኪ: እንዘ ንሰግድ ንብለኪ . . .)
የደረሷት እርሳቸው ናቸው:: ትልቁን መልክአ ማርያምም ደርሰዋል:: ይህ መልክእ ጣዕሙ ልዩ ነው::
የጻድቁ ንጉሥ ሚስት (ማርያም ክብራ): ልጆቻቸው (አፄ ልብነ ድንግልና ቡርክት ሮማነ ወርቅ) እጅግ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩ:: ንጉሡ አፄ ናዖድ ከባለሟልነት የተነሳ ድንግል ማርያምን "እመቤቴ ስምንተኛው ሺ መቼ ይገባል? ጊዜውስ እንዴት ያለ ነው?" አሏት::
እመ ብርሃንም በአካል ተገልጻ የዘመኑንና የሰውን ክፋት ነገረቻቸው:: ንጉሡም አዝነው "እመቤቴ! ከዛ ዘመን አታድርሺኝ" አሏት:: በዚህ ምክንያት የስምንተኛው ሺህ ዘመን መስከረም 1 በ1500 ዓ/ም ሊገባ እርሳቸው ነሐሴ 7 ቀን በ1499 ዓ/ም ዐርፈዋል::
††† ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የድንግል እናቱን ጣዕም: ፍቅር: የቅዱስ ጴጥሮስን ሃይማኖትና የአፄ ናዖድን በረከት ያሳድርብን::
††† ነሐሴ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓለ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ገብርኤል መበሥር
4.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
5.አፄ ናዖድ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
6.ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ (ወልደ ያዕቆብ-ልደቱ)
7.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
††† "መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው:: ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል::
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው . . .
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::" †††
(መዝ. ፹፮፥፩-፮)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
✞✞✞ እንኩዋን ለቅድስት #እናታችን_ማርያም_መግደላዊት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
✞✞✞ #ቅድስት_ማርያም #መግደላዊት ✞✞✞
=>ይህችን ቅድስት "ማርያም" ያሏት ወላጆቿ ሲሆኑ "መግደላዊት" እያሉ የጠሯት ደግሞ ሐዋርያት (ወንጌላውያን) ናቸው:: ለምን እንዲህ ብለው ጠሯት ቢሉ:- በዘመኑ "ማርያም" የሚባሉ ብዙ ሴቶች ነበሩና ከእነሱ ለመለየት ነው:: አንድም ሃገሯ ከእሥራኤል አውራጃዎች በአንዱ (በመግደሎን) ተወልዳ ያደገች ናትና::
+ማርያም መግደላዊት ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ነበረችና ሰዎች ያደንቁዋት: ወንዶች ይከተሏት ነበር:: በዚህም 7 አጋንንት ተጠግተው 7 ዓይነት ኃጢአትን ያሠሯት ነበር:: በተለይ ደግሞ በዝሙት: በትውዝፍት (ምንዝር ጌጥ) እና ትዕቢት በእጅጉ የታወቀች ነበረች::
+በእንዲህ ያለ ግብር ጸንታ ለዘመናት ኖረች:: በዚያ ወራት የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋችንን ተዋሕዶ ያስተምር ነበርና ስለ እርሱ ሰማች:: "ጌታ ኃጥአንን አይጸየፍም (ይቀበላል): አጋንንትንም ያስወጣል" ብለውም ነገሯት:: ጥሪው የእግዚአብሔር ነውና ማርያም መግደላዊት አልዘገየችም::
+ወደ እርሱ ሔዳ ጌታ ባያት ጊዜ ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና አቀረባት:: በቸርነቱም ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ የሞሉትን 7 የአጋንንት ነገድ አስወጣላት:: በዚያች ሰዓት ዕለቱኑ እንደተወለደ ሕጻን ከነበረባት ችግር ሁሉ ንጹሕ ሆነች:: ጌታም ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ትሆን ዘንድ መርጦ ተከታዩ አደረጋት::
+ቅድስት ማርያም ከዚህች ቀን ጀምሮ ፍጹም ተቀየረች:: እርምጃዋ ሁሉ የተባረከና የንጽሕና ሆነ:: ጌታን እስከ ዕለተ ሕማሙ ድረስ በመዓልትም: በሌሊትም በቅን አገለገለችው::
ጌታችን ስለ እኛ መከራን በተቀበለባት በዚያች ዕለተ ዐርብም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ከጐኑ ነበረች::
+ከግርፋቱ እስከ ስቅላቱ እያለቀሰች ተከትላዋለች:: በእግረ #መስቀሉ ያለቅሱ ከነበሩ ቅዱሳት አንስትም አንዷ እርሷ ነበረች:: (ዮሐ. 19:25) ቅዱሳኑ #ዮሴፍና #ኒቆዲሞስ ጌታን ሲቀብሩትም ከእሕቶቿ ጋር አብራ ተከትላ አይታለች::
+እሑድ በሌሊት: ገናም ሳይነጋ መቃብሩን ታይ ዘንድ: ሽቱም ልትቀባ ወደ ጐልጐታ ገሠገሠች:: ፍጹም የአምላክ ፍቅር አድሮባታልና ግርማ ሌሊቱንና የአይሁድ ጭፍሮችን አልፈራችም:: ጌታችንም #ክእመቤታችን ቀጥሎ ከፍጥረት ወገን ትንሳኤውን ያየች የመጀመሪያዋ ሰው ትሆን ዘንድ አደላት::
+በመቃብሩ ራስጌና ግርጌም 2 መላእክትን (#ሚካኤልና_ገብርኤልን) ተመለከተች:: ዘወር ስትል ደግሞ የክብርን ባለቤት አየችው:: አላወቀችውምና "ማርያም" አላት:: "ረቡኒ-ቸር መምሕር ሆይ" ብላ ሰገደችለት::
+ጌታም "ሑሪ ኀበ አኀውየ ወበሊዮሙ . . . ሒደሽ ለደቀ መዛሙርቴ በያቸው . . . " ብሎ የትንሳኤው ሰባኪ አደረጋት:: "ወሖረት ወነገረቶሙ ለአርዳኢሁ . . . " እንዲል ትንሳኤውን ለደጋጉ #ሐዋርያት ሰበከችላቸው::
+#ቅድስት_ማርያም መግደላዊት ከክርስቶስ ትንሳኤ በሁዋላ ለ40 ቀን #መጽሐፈ_ኪዳንን: #ትምሕርተ_ኅቡዓትን ተምራለች:: በዕርገቱ ተባርካ: በበዓለ ሃምሳ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ተካፍላለች:: በአዲሲቷ #ቤተ_ክርስቲያን ውስጥም ልዩ አገልግሎት ነበራት::
+ቅዱሱ #እስጢፋኖስ 8 ሺውን ማሕበር ሲመራ ሴቶችን ታስተዳድርለት ነበር:: ከሁሉ በላይ ግን ቅድስቲቱ የቅዱሳን ሐዋርያት መጋቢ ነበረች:: በዘመኑ #መንፈስ_ቅዱስ የሚባርከውን #አጋፔ (የፍቅር ማዕድ) የምታዘጋጀው እርሷ ነበረች::
+እንዲያውም አንዴ የሚበላ ጠፍቶ ለሐዋርያት ማዕድ ፍለጋ በሔደችበት እግሯ ቆስሎና ደምቶ መመለሷ ይነገራል:: እንዲህ አድርጋ ያዘጋጀችውን ማዕድ #ቅዱስ_መልአክ ወርዶ ወደ ሰማይ ወስዶታል:: ለቅዱሳን ሐዋርያትም እያመጣ ይመግባቸው ነበር::
+እናታችን #ማርያም_መግደላዊት በስብከተ ወንጌልም የተመሰከረላት ነበረች:: የመጀመሪያዋ የሐዲስ ኪዳን #ዲያቆናዊት ሴት ስትሆን ክርስትናንም ተዟዙራ ሰብካለች:: ስለ ቅዱስ ስሙም ሽሙጥን: ስድብን: መንገላታትን እና ግርፋትን ታግሳለች::
+በተለይ አይሁድ ብዙ አሰቃይተዋታል:: ቅድስቷ እናታችን መልካሙን ገድል ተጋድላ በበጐ እድሜ በዚህች ቀን ሔዳለች:: በዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ (ከአንዳንዶቹ በቀር) ያከብሯታል::
+"+ #ቅድስት_ኢየሉጣ_ዘቂሣርያ +"+
=>በቀድሞው የግሪክ ግዛት (ቂሣርያ ውስጥ) በዘመነ ሰማዕታት አካባቢ የነበረችው #ቅድስት_ኢየሉጣ ክርስትናን የወረሰችው ከወላጆቿ ነው:: ገና ወጣት እያለች ወላጆቿ በማረፋቸው የሃብታቸው ወራሽ ሆነች::
+ነገር ግን አንድ ክፉ ሰው መጥቶ ሃብቷን ነጠቃት:: በዚህ አዝና "የዳኛ ያለህ" ልትል ወደ ፍርድ ቤት ስትሔድ የጠበቃት ግን የሚገርም ነበር:: የተገፋችው እርሷ ተከሳሽ: ገፊው ደግሞ ከሳሽ ነበር:: የክሱ ጭብጥ ደግሞ "ክርስቲያን ነሽ" የሚል ነበር::
+በወቅቱ በመኯንንቱ ፊት ክርስትናዋን ብትክድ በቀጥታ ሃብቷን ማግኘት ትችል ነበር:: እርሷ ግን ለአፍታ አሰበች:: "እንዴት ዘላለማዊ ሃብቴን (ሃይማኖቴን) በኃላፊው ንብረት እለውጣለሁ" ብላ ሁሉም እየሰሙ ጮክ ብላ "#ክርስቲያን_ነኝ" አለች::
+ወዲያውም ሞት ተፈርዶባት ተገደለች:: ታላቁ #ቅዱስ_ባስልዮስ ስለ #ሰማዕታት በጻፈው ድርሳን ላይ በስፋት አመስግኗታል:: ለሴቶችም ታላቅ ምሳሌ ናት ብሏታል::
=>ቅዱሳት እናቶቻችንን ያጸና ቸር አምላካቸው እኛንም በሃይማኖትና በምግባር ያጽናን:: ከበረከታቸውም አብዝቶ ያድለን::
=>ነሐሴ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ማርያም መግደላዊት (ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት)
2.ቅድስት ኢየሉጣ ሰማዕት (ዘቂሣርያ)
3.አባ ዊጻ (የታላቁ ሲኖዳ ደቀ መዝሙር)
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል
=>+"+ #ጌታ ኢየሱስም:- "#ማርያም" አላት:: እርሷ ዘወር ብላ በእብራይስጥ:- "#ረቡኒ" አለችው:: ትርጉዋሜውም "መምሕር ሆይ!" ማለት ነው:: ጌታ ኢየሱስም:- "ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ:: ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሔደሽ . . . ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው" አላት:: #መግደላዊት_ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይሕንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች:: +"+ (ዮሐ. 20:16)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† እንኩዋን ለጻድቃን ቅዱሳን #አባ_አብርሃም: #ቅዱስ_ዮሐንስ እና #አባ_ፊልዾስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††
††† #አባ_አብርሃም_ክቡር ገዳማዊ †††
=>ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆን በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ከተነሱ ከዋክብት አንዱ ነው:: #ክርስቲያን ወላጆቹ በሥርዓት አሳድገው "ሚስት አግባ" አሉት:: እሺ እንዳይላቸው ከልጅነቱ ጀምሮ የተመኘው ምናኔ ሊቀርበት ሆነ:: እንቢ እንዳይላቸው ደግሞ ወላጆቹ ያዝናሉና የልቡን በልቡ ይዞ "እሺ" አላቸው::
+ሠርግ ተደግሶ: #ተክሊል ተደርሶ: ከአንዲት ክርስቲያን ጋር አጋቡት:: በጋብቻው ማግስት ግን ከነ ድንግልናው ጠፍቶ በርሃ ገባ:: በዚያም አንዲት በዓት አዘጋጅቶ ፈቃደ ሥጋውን እየቀጣ: ፈቃደ ነፍሱን እያለመለመ ለ10 ዓመታት ተቀመጠ::
+በነዚያ ሁሉ ዘመናት የሞቀ አልለበሰም: የላመ የጣመ ነገር አልበላም:: የፀሐይ ብርሃን እንኩዋ አልተመለከተም:: በዚያ ወራትም ወሬ ነጋሪ ወደ በዓቱ መጥቶ "ወላጆችህ ዐረፉ:: በቤት ውስጥ ከ6 ዓመት እህትህ ከማርያ በቀር ማንም የለምና የወላጆችህን ሃብት ውረስ" አለው::
+አባ አብርሃም የሚያደርገውን ያውቃልና ከበርሃ ወጥቶ ወደ ሃገር ቤት ሔደ:: ትንሽ እህቱን (6 ዓመቷ ነበር) ለቤተ ዘመድ አደራ ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን አንድ ሳያስቀር ለነዳያን በትኖ:ወደ በዓቱ ተመለሰ:: በዚያም እንዳስለመደ በጾምና ጸሎት ተወስኖ ለ10 ዓመታት ቆየ::
+ተጋድሎ በጀመረ በ20 ዓመቱ #እግዚአብሔር ለሌላ አገልግሎት ጠራው:: የግብጽ ሊቀ ዻዻስ #አባ_አብርሃምን አስመጥቶ ቅስናን ሾመውና "ሒደህ ወንጌልን ስበክ" አለው:: ችግሩ እርሱ የተላከባት ሃገር አንድም ክርስቲያን የሌለባት ከመሆኗ በባሰ እጅግ ጨካኝ ናቸው::
+ማንም ደፍሮ በዚያ ሃገር ውስጥ ነገረ እግዚአብሔርን የሚናገር ሰው አልነበረም:: አባ #አብርሃም ወደ ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው እንደ ልማዳቸው መሬት ላይ ጥለው ደበደቡት: አጥንቶቹንም ሰባበሩት:: ሞቷል ብለው ከከተማ ውጪም ጣሉት::
+እርሱ ግን በፈጣሪው ኃይል ጸንቶ ተነሳ:: ማስተማሩ ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን ተረድቷልና ስለ እነሱ ተግቶ ይጸልይ ጀመር:: አሕዛብ ጠዋት ቢመጡ በከተማዋ መሐል ላይ ሲጸልይ አገኙት:: ስለ ተናደዱ ድጋሚ አካሉን በዱላ ሰባብረው እየጐተቱ ከከተማ አስወጡት:: በዚያም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት::
+ነገር ግን ጠዋት ሲመለሱ እዛችው ቦታ ላይ ሲጸልይ አገኙት:: ይሕ የሚደረገው ለእነርሱ ድኅነት መሆኑን አልተረዱምና እነርሱ በየቀኑ እየደበደቡና እያሰቃዩት እርሱ ስለ እነሱ እየጸለየ 10 ዓመታት አለፉ:: ቅዱሳን ተስፋ አይቆርጡምና በመጨረሻው ተሳካለት::
+የቅዱሱ የዘመናት ጸሎት ፍሬ አፍርቶ እግዚአብሔር በአሕዛብ ልቡና ያደሩ አጋንንትን አራቀለት:: አንድ ቀን ጠዋት የሃገሩ ሕዝብ ሁሉ (ወንዱ: ሴቱ: ትልቁ: ትንሹ) ወደ ጻድቁ መጸለያ መጡ:: ለእርሱስ የጠብ መስሎት ነበር:: እነርሱ ግን በአንድነት በፊቱ ተንበርክከው ሰገዱ:: ይቅር እንዲላቸውም ለመኑት::
+ቅዱሱ ይሕንን ሲመለከት ሐሴትን አደረገ:: ሁሉንም #በስመ_ሥላሴ አጥምቆ ክርስቲያን አደረጋቸው:: አብያተ ክርስቲያናትንም አነጸላቸው:: በሁዋላ ግን በጣም ሲወዱትና ሲያከብሩት ተመልክቷልና ከውዳሴ ከንቱ (#ስብሐት_ብጡል) መለየት ፈለገ:: ፈጣሪንም በቸርነቱ እንዲጠብቃቸው ለምኖ: በሌሊት ጠፍቶ ወደ ነበረበት በርሃ ገባ::
+እርሱ በበርሃ ሁኖ ስለ ትንሽ እህቱ #ማርያ ያስብ ነበርና አስጠራት:: "ምን ትፈልጊያለሽ?" አላት:: እርሷም "እንዳንተ መሆን" ስላለችው አስተምሮ: ፈትኖ አመነኮሳት:: ለጥቂት ዓመታት በሥርዓት ከኖረች በሁዋላ ግን ችግር ተፈጠረ::
+ከአንድ መነኩሴ ጋር በነበራት ያልተገባ ቅርርብ የዝሙት ፍላጐታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በኃጢአት ወደቁ:: በዚህ ተስፋ ቆርጠው 2ቱም ቆባቸውን ጥለው ከተማ ገቡ:: ይልቁኑ እርሷ (ማርያ) ሴተኛ አዳሪ ሆነች::
+በዚያ ሰሞን ቅዱሱ አብርሃም ራዕይን ያያል:: ትልቅ ዘንዶ አንዲት ርግብን ሲውጣት: መልሶም ሲተፋት አይቶ እሕቱ መሆኗን ተረዳ:: ወዲያው ጥሩ ልብስና ፈረስ ተውሶ ተነሳና ወደ ከተማ ገባ:: የጦር መኮንን መስሎ እህቱ ቤት ገባ::
+ሸሽታ እንዳታመልጠው ቤቱን ዘጋና ራሱን ገለጠላት:: ደንግጣ እንደ በድን ብትሆንም እርሱ አረጋጋት:: "እህቴ! ንስሃ ግቢ: አምላክ ይራራልሻል" አላት:: ልቧ ወደ ምክሩ አዘንብሏልና የእህቱን ነፍስ ማርኮ ወደ ገዳም ተመለሰ::
+በዚያ በዓት ሠርቶላት: ቀኖናም ሰጥቷት ሔደ:: #ማርያም ስለ ኃጢአቷ ፈንታ የምትገርም የቅድስና ሰው ሆነች:: ያየ ሁሉ እየተደነቀባት ከዓመታት ተጋድሎ በሁዋላ ዐረፈች:: አባ አብርሃም በተረፈ ዘመኑ በንጹሕ ገዳማዊ ሕይወት ተጠምዶ ኑሯል::
+በዘመኑ ሁሉ በጥርሱ ስቆ: በከንፈሩም አልባሌ ነገርን ተናግሮ አያውቅም:: ልቡ በፈጣሪው ፍቅር የታሠረ ነበርና ሕማማተ ክርስቶስን እያሰበ እንባው ያለማቁዋረጥ ይፈስ ነበር:: ደግና ቅዱስ ሰው አብርሃም በዚህች ቀን ዐርፎ ተቀብሯል::
††† #ቅዱስ_ዮሐንስ_ጻድቅ †††
=>ይህ ቅዱስ የነበረው በዘመነ ሰማዕታት ቢሆንም እንደ ሰማዕታት ስቃይ አልደረሰበትም:: ክርስቲያኖችን እንዲገድሉና አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያቃጥሉ ከተመደቡ ወታደሮች አንዱ ነበረ:: ታዲያ እንዲገድላቸው የሚሰጡትን ክርስቲያኖች እየወሰደ ይደብቃቸው ነበር::
+የመከራው ዘመን እስኪያልፍ ድረስም ይንከባከባቸው ነበር:: ሌሎች ወታደሮች እንዳይነቁበት ሁሌም "ክርስቲያኖችን በጣም እጠላለሁ" እያለ ያወራ ነበር:: እርሱ በሌሊት ሁሌም ለጸሎት ይተጋ ነበር:: በእንዲህ ያለ ግብር ኑሮም በዚህች ቀን በሰላም ዐርፏል::
††† #አባ_ፊልዾስ #ዘደብረ_ቢዘን †††
=>#ደብረ_ቢዘን በቀድሞ የኢትዮዽያ ክፍለ ሃገር (አሁን #ኤርትራ) ውስጥ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው:: ገዳሙ #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም በስደቷ ያረፈችበት: ጌታችን የባረከውና የመረጠው ቦታ ነው:: #አባ_ዮሐንስን: #አባ_ናርዶስንና ሌሎች ከዋክብት አበውን ያፈራ ሲሆን የአባ ፊልዾስን ያሕል ግን አልተገኘም::
+ጻድቁ በግል የተጋድሎ ሕይወታቸው: ገዳሙን በአበ ምኔትነት በመምራታቸውና በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ምስጉን ነበሩ:: እርሳቸው ቅዱስ ሆነው አልበቃቸውምና ብዙ ቅዱሳንን ወልደዋል:: ይሕች ዕለትም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ናት::
=>አምላከ ጻድቃን ገዳማትን ከመከራ ይጠብቅልን:: ከአባቶቻችን ቅዱሳን ጸጋ በረከትንም ይክፈለን::
=>ነሐሴ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ አብርሃም ገዳማዊ
2.ቅድስት ማርያ እህቱ
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ
4.አባ ፊልዾስ ዘደብረ ቢዘን
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
6.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)
=>+"+ በድካም: አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ. . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው:: +"+ (2ቆሮ 11:23)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
በቅዱሳን አድሮ የሚኖር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ሰው ኹኗዋልና በሞተ ሥጋ፣ በሞተ ነፍስ ለነበሩ ሰዎች ልጅነት ተሰጣቸው /ዮሐ.፩፡፲፫/፡፡ በኃጢአት በክሕደት ለነበሩ ሰዎች ሃይማኖት (አሚን) ተሰጣቸው /ማቴ.፬፡፲፬/፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ይህን ድንቅ ምሥጢር ኑ እዩ፡፡ ስለ ተገለጸን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፡፡ ከዚህ ቀደም ሰው ኾኖ የማያውቀው እንግዲህም ወዲህ ሰው ማይኾነው ሰው ኾኗልና ይህን ድንቅ ምሥጢር ኑ እዩ፡፡ ቃል ከሥጋ ጋር ቢዋሐድ ጥንት የሌለው መለኮት ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ዘመን ተቀድሞት ወደ ኋላ ተገኘ፡፡
ቅድምና የሌለውም ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ተባለ፡፡ አንድም ጥንት (ቅድምና) የሌለው ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ተባለ፡፡ ዘመን
የማይቆጠርለትም መለኮት ፲፪ ዓመት ኾነው /ሉቃ.፪፡፵፪/፤ ፴ ዓመት ሞላው ተብሎ ዘመን ተቆጠረለት /ሉቃ.፫፡፳፫/፡፡ አንድም አካላዊ ቃል በጎላ በተረዳ ሰው ኹኗልና በኵር ያልነበረ መለኮት በኵር ተባለ /ማቴ.፩፡፳፭/፡፡ ክብር የሌለውም ሥጋ ክቡር አምላክ ተባለ፡፡ በገዥነት የማይታወቅ ሥጋ በገዥነት ታወቀ፤ በተገዢ ሥጋ ታይቶ የማይታወቅ መለኮትም በተገዢ ሥጋ ታየ፡፡ ቅድመ ዓለም የነበረው፣ በማዕከለ ዓለም ያለው፣ መቼም መች የሚኖረው ኢየሱስ ከርስቶስ እንሰግድለትና
እናመሰግነው ዘንድ ከአብ ከባሐርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ አንድ ባሕርይ ነው፡፡
ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ አንድ ባሕርይ ከሚኾን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንደይነሣን ለምኚልን፡፡
፯. ነቢዩ ሕዝቅኤል የእርሷን ነገር “በድንቅ ቁልፍ የተቈለፈች ደጅ በምሥራቅ አየሁ” ብሎ ተናገረ /ሕዝ.፵፬፡፩-፪/፡፡ ከእግዚኣ ኃያላን በቀር ሳይከፍታት ገብቶ ሳይከፍታት የወጣ የለም፡፡ እግዚአ ኃያላን እሱ ሳይከፍታት ገብቶ ሳይከፍታት ወጣ እንጂ፡፡
እግዚአ ኃያላን ከሚባለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን አንዳነሣን ለምኚልን፡፡
፰. ኆኀትም (ድጅም) የተባለች መድኃኒታችንን ጌታን የወለደችልን ድንግል ናት፡፡ እሱን ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለቸና፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም፡- “… አንተ መናገር የተሰጣቸውን ሠረገሎች ድምፅ የሰማህ ባለ ሞገስ ሆይ (ሕዝ.፫፡፲፫)! እንደዚሁም የክንፎቻቸውን ድምፅና የዚያን ሠረገላ ታላቅ እንቅስቃሴ የሰማህ ሆይ (ሕዝ.፲፡፭)! አንተ የኪሩቤልን መልክ
መለወጥ ያየህ የበራልህ ነፍስ ሆይ! እንዲሁም እኒያ የእሳት ላንቃዎች በከፍታ ላይ የተቀመጠውን ሲያመሰግኑ የሰማህ ሕዝቅኤል ሆይ (ሕዝ.፩፡፬-፳፰) ና! አንተ የቡዝ ልጅ ሆይ (ሕዝ.፩፡፳፫) ና! የተጠቀለለውን የትንቢትህን ቃል ብራና አምጣልን፡፡ አንተ ቁምና እውነትን ተናገር፤ ሌሎቻችን ኹሉ ዝም እንበል፡፡ ካየኻቸው ራዕዮች መካከል ድንግል ማርያም ታይታህ እንደኾነ፤ ፍጥረት ኹሉ ውበቷን ያይ ዘንድ መልኳን ግለጥልን፡፡ በትንቢትህ ውስጥ የጌታህን እናት
የሚመለከት አንዳች ነገር ካለ ይህ ለሚሰሙት እጅግ ውድ ስለኾነ ተነሣና አብራራልን፡፡ ይህም ያም (መናፍቅ) ከመውለዷ በኋላ ድንግል አልነበረችም በማለት ይናገራልና እውነት ድንግልናዋን አጥታ እንደኾነ እስኪ አንተ አስረዳን፡፡ ሕዝቅኤል ሆይ! ዛሬ የአንተ ተራ ነውና እስኪ ተናገር፡፡ ስለ እመቤታችን ማርያም ተናገርና ከንቱ ምርምሮችን ግታልን፡፡
እስከ አሁን በትንቢት ተነግሮ የነበረው ምን እንደነበር እንስማ፡፡
የማትመረመር ስለኾነችው ስለ ድንቅ እናታችን ይህ ነቢይ በትንቢቱ ውስጥ እንዲህ ተናግሮ ነበር፡- ‘ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር።
እግዚአብሔርም። ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።’ አንተ የመንፈስ ነቢይ ሆይ! ይህ ቃል ምን ማለት እንደኾነ እስኪ ገልጠህ አብራራልን፡፡ በትንቢት የተነገረው የተዘጋው በር ድንግል
ማርያም ናት፡፡ ምክንያቱም መሲሑ ጌታ በእርሱ በኵል ወደ ዓለም መጥቶ ዝግ አድርጎ ትቶታልና፡፡ ጌታ በዚህ በር ሲገባ እንዳልከፈተው ዕብራዊ የኾነ ሕዝቅኤል ከእኛ ጋር አብሮ ይህንኑ ይመሰክራል፡፡
እግዚአብሔር እንደወደደው በመውለድ በር ወደ ዓለም ገባ፡፡ ያንንም በር በድንግልና ዘጋው፡፡ ነቢዩ በሩ ተዘግቶ ያየው ያ ቤተ መቅደስ ስለ ድንግልናና ስለማይለወጥ ድንግልናዋ የሚያሳየን ነው፡፡ ቅዱሱ መሲሑ
(ክርስቶስ) ሲኾን ቤተ መቅደሱም ማርያም ናት፡፡ የተዘጋውም በር በእርሷ የሚኖረውና ተፈትሖ የሌለበት የድንግልዋ ማኅተም ነው” ብሏል /Jacob of Serug, Homily on the Perpetual Virginity of Mary, pp VII-X/፡፡
የማኅፀንሽ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል ነው፡፡ ለሰው ከማያዝን ከማይራራ፤ አንድም ለእርሱ ከሥላሴ ዘንድ ምሕረት ከሌለው፤ አንድም ኃጢአቱን ሸልጎ ከማይሠራ ከዲያብሎስ እጅ ያዳነን ጌታችንን የወለድሽው ሆይ! በደንግሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ፍጽምት ነሽ፡፡
መርገም ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለብሽ /ኢሳ.፩፡፱/ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እያማለድሽ የምታሰጭ ነሽ፡፡ ጌትነቱ እንደ ነገሥታት በጉልበት፣ እንደ ካህናት በሀብት፣ እንደ ጣዖታትም በሐሰት ባይደለ በክብር ባለቤት ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሸልና በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ኹሉ ይልቅ ክብር ላንቺ ይገባል፡፡ አካላዊ ቃል መጥቶ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ ሰው ሰውኛውንም ኖረ፡፡ መሐሪ፣ ይቅር ባይ፣ ሰው የሚወደው ሰው ወዳጅ ነውና በልዩ አመጣጡ መጥቶ አዳነን፡፡ “አኮ በተንባል ወአኮ በመልአክ አላ ለሊሁ እግዚእ መጸእ ወያድኅነነ - በአማላጅ አይደለም፤ በመልአክም አይደለም፡፡ እርሱ ራሱ፣ በራሱ ደም፣ በራሱ ሊቀ ካህንነት መጥቶ ያድናቸዋል እንጂ ” /ኢሳ.፷፫፡፱/ እንዲል እንደ ቀደመው በረድኤት ሳይኾን በኩነት (ሰው ኹኖ) መጥቶ አዳነን፡፡ አንድም አምስት ሺሕ ካምሰት መቶ ዘመን ሲፈጸም አንድ ሰዓት ስንኳ ሳያሳልፍ በጽኑ ቀጠሮው መጥሮ አዳነን፡፡
በጽኑ ቀጠሮ መጥቶ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡
✞✞✞✞✞ሰናይ ሚዲያ✞✞✞✞✞
የዩቲዩብ እና የቴሌግራም ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
https://www.youtube.com/channel/UCFZrceurPVvpMGNHzpGdZqA
ቴሌግራም
/channel/+NffLVRu3-eBjNTI0
https://www.facebook.com/mesfen.nahusenay
የረቡዕ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ
✞✞✞✞✞ሰናይ ሚዲያ✞✞✞✞✞)፡- Telegram /channel/+NffLVRu3-eBjNTI0
ለምስጋና ሦስተኛ፣ ለፍጥረት አራተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ዕለት ከወትሮ ይልቅ መላእክትን አስከትላ እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡
ከባረከችው በኋላም ምስጋናዋን “ኵሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብፅዕት አንቲ…” ብሎ ይጀምራል፡፡
፩. ኵሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብፅዕት አንቲ ሰማይ ዳግሚት ዲበ ምድር - ከምድር በላይ ያለሽ ኹለተኛ ሰማይ ሆይ! በሦስቱ ሰማያት (በኢዮር፣ በራማ፣ በኤረር) ያሉ መላእክት ንዕድ ነሽ፤ ክብርት ነሽ ይላሉ፡፡ ማርያም የምሥራቅ ደጅ ናት፤ ከእርሷ የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ ተገኝቷልና፡፡ ማርያም ሙሽራዋ ንጹሕ የሚኾን ንጽሕት የሠርግ ቤት ናት፡፡
በሠርግ ቤት የመርዓዊና የመርዓት (የሙሽራና የሙሽሪት) ተዋሕዶ ይደረግበታል፡፡ በእመቤታችንም እንደ መርዓዊና እንደ መርዓት ተዋሕዶ፤ ትስብእትና መለኮት አንድ ኹነዋልና፡፡ በሠርግ አዝማደ መርዓዊና አዝማደ መርዓት አንድ እንዲኾኑባት በእመቤታችንም ምክንያት ሰውና መላእክት፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ ኹነዋልና እመቤታችን ንጽሕት የሠርግ ቤት ናት /ኤፌ.፪፡፲፭/፡፡ አባ ሕርያቆስ “አስተንፈሰ ወአጼነወ ወኢረከበ ዘከማኪ፤
ወሠምረ መዓዛ ዚኣኪ ወአፍቀረ ሥነኪ ወፈነወ ኀቤኪ ወልዶ ዘያፈቅር” እንዲል /ቅዳ.ማር.ቁ.፳፬/ አብ ከሰማይ ኾኖ አየ፤ ነገር ግን እንዳንች ያለ ባያገኝ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን ልጁን ሰዶ ካንቺ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡
ተቀዳሚ ተከታይ ከሌለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት (ክብርት) በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
እዚህ ጋር አንዳንድ ወገኖች የሚያነሡትን ጥያቄ መልሰን እንለፍ፡፡
“ልመናስ ከዚያ በኋላ ስንኳን በሷ (ከበቁ በኋላ) በሌሎችም የለባቸውም፡፡ በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ አለ እንጂ” ስለተባለ ምሥጢሩን ሳይረዱ “ቅዱሳን በአጸደ ነፍስ አያማልዱም” ለማለት የሚጠቅሱት ወገኖች አሉ፡፡ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜ ግን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበት በ፲፫ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “ጻድቃን ይረክቡ ኵሎ በአሐቲ ተምኔቶሙ በአሐቲ ስእለት - ጻድቃን አንድ ጊዜ በለመኑት ልመና የሚሹትን ኹሉ ያገኛሉ” እንዳለው /ቁ.፻፶፱/ ቅዱሳኑ በአጸደ ሥጋ ሳሉ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ “በስምሽ/ህ ለታረዙ ያለበሰ፣ ሕሙማንን የጐበኘ፣ ዝክርሽ/ህን የዘከረ…” እያለ በገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት በስማቸው የዘከረ፣ በስማቸው ሕሙማንን የጐበኘ፣ የመጸወተ እንደሚምርላቸው የሚያስረዳ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር፣ ዓለምን ዳግም በንፍር ውሃ የማያጠፋትና በየዕለቱ ቀስተ ደመናን የምንመለከተው ፡- “ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ኹሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይኾንም” ብሎ /ዘፍ.፱፡፲፩/ ለኖኅ አንድ ጊዜ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት እንጂ ኖኅ በየዕለቱ እንዲህ ስለሚለምን አይደለም፡፡ “አይለምንም” ሲባል ግን ክብሩን፣ ልዕልናውን፣ መንፈሳዊ ብቃቱን የሚያስረዳ እንጂ ማማለድ አይችልም ለማለት አይደለም፡፡ እንደውም ይህ ኃይለ ቃል ከማማለድ በላይ የኾነ ክብር እንደተሰጣቸው የሚያመለክት ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ጊዜ ለምኖ በየጊዜው የሚሹትን ማግኘት፤ ዕለት ዕለት እየለመኑ የሚሹትን ከማግኘት በላይ ልዕልናን፣ ክብርን፣ መንፈሳዊ ብቃትን ያሳያልና፡፡ አሁን ቅዱሳንን አማልዱን ስንላቸው አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ደጋግሞ
እንደገለጸው ቃል ኪዳናችሁን አሳስቡልን ስንል ነው /ቅዳ.ማር.ቁ.፻፷፬-፻፸፩ ይመልከቱ/፡፡
፪. ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገር - ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ፡፡
አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! አንቺን ብቻሽን ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ካም፣ ትውልደ ያፌት (ትውልድ ኹሉ) ያመሰግኑሻል /ሉቃ.፩፡፵፰/፡፡ ፱ ወር ከ፭ ቀን ማኅፀንሽን ዓለም አድርጐ የኖረብሽ ሀገረ እግዚአብሔር፣ መንግሥተ ሰማያት ሆይ! ነቢያት ላንቺ “ኢይትዐፀዉ አናቅጽኪ (በሮችሽ ኹል ጊዜ ይከፈታሉ - ንስሐ የሚገቡ ኃጥአንን ለመቀበል)፤ ወኢይጸልም ወርኅኪ (ጨረቃሽ አይቋረጥም)፤ ወኢየዐርብ ፀሐይኪ (ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም - ፈጣሪሽ አያልፍም)፤
እስመ እግዚአብሔር ብርሃንኪ ለዓለም (ለዘለዓለም ብርሃንሽ እግዚአብሔር ነውና)” /ኢሳ.፷፡፲፩፣፳/፤ “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! ስላንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ (ልዩ) ነው” /መዝ.፹፮፡፫/ እያሉ ድንቅ ድንቅ ነገርን ተናገሩልሽ፡፡ በርግጥም ሰማይና ምድር የማይችሉትን አምላክ የአንቺን ማኅፀን ከተማ አድርጎ ፱ ወር ከ፭ ቀን መኖሩ፤ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ አካላዊ ቃልን መፀነስሽ፤ በኅቱም ድንግልና መወለዱ፤ የድንግልና ጡቶችሽን ማጥባትሽ ድንቅ ነው፡፡ ደስ ብሏቸው የሚኖሩ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት ማደሪያ ኹነሻልና የምድር ነገሥታት ይህን ዜናሽን ሰምተው፣ ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን ዐውቀው መንነው ይሄዳሉ፡፡ እነርሱ ብቻ አይደሉም፤ ሠራዊቶቻቸውም ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን ዐውቀው መንነው ይሄዳሉ፡፡ አንድም ብርሃን ልጅሽን አምነው ጸንተው ይኖራሉ፡፡ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! አንቺን ብቻሽን ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ካም፣ ትውልደ ያፌት ያመሰግኑሻል /ሉቃ.፩፡፵፰/፤ ካንቺ ለተወለደውም ይሰግዱለታል፤ “ዐቢይ እግዚአብሔር - እግዚአብሔር ታላቅ ነው” እያሉም ያከብሩታል፤ ያገኑታልም፡፡
“ዐቢይ እግዚአብሔር” እያሉ ከሚያከብሩት ከሚያገኑት ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፫. “እንተ በአማን ንጹሕ ዝናም” የተባለ፣ የነፍሳትን ጥም ያበረደ የሕይወት ዝናም፣ የሕይወት ጠል፣ የሕይወት ውሃ ክርስቶስን ቋጥረሽ (በድንግልና ፀንሰሽ፣ በድንግልና ወልደሽ) የታየሽልን እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም፡- “ንዑ እንከ ከመ ናልዕላ ለዛቲ ደመና ብርሃን እንተ ጾረቶ ለማየ ዝናም ንጹሕ- ንጹሑን የዝናም ውሃ የተሸከመችውን የብርሃን ደመና ኑ ከፍ ከፍ እናድርጋት” ብሎ ጋብዞናል /አርጋኖን ዘሠሉስ ፮፡፪/፡፡ ስትወልጂው ማኅተመ ድንግልናሽ አለመለወጡ፤ አካላዊ ቃል ሰው ሲኾን
አምላክነቱ ላለመለወጡ፣ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባዪ መኖርሽም ልጅሽ አምላክ ወሰብእ (ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው) ሲባል ለመኖሩ ምሳሌ ነውና አብ የልጁ ምልክት አደረገሽ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ቢያድርብሽ፣ ኀይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ቢለብስ፤ አንድም መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ ግብራት (ማለትም ከሩካቤ፣ ከዘር፣ ድንግልናን ከመለወጥ) ቢከለክልሽ፣ ኀይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ ግብራት ቢከልልሽ ለዘላለሙ የሚኖር አካላዊ ቃልን ወለድሽልን /ሃይ.አበ.፻፲፡፳፱/፡፡ እርሱም ሰው ኾኖ ከኃጢአት አንድም ከኃጢአታችን ፍዳ አዳነን፡፡
✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳት #እናቶቻችን #አትናስያ_እና_ኢዮዸራቅስያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
✞✞✞ #ቅድስት_አትናስያ ✞✞✞
=>የዚህች ቅድስት ሕይወት በብዛት የእግዚአብሔርን ቸርነትና የንስሃን ፍጹምነት የሚያሳይ ነው:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
+ቅድስት አትናስያ ግብፃዊት ስትሆን የነበረችውም #መኑፍ በሚባል አውራጃ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ይህ ዘመን "ዘመነ ከዋክብት" ይባል ነበር:: ከቁጥር የበዙ ቅዱሳንም በዘመኑ ነበሩ::
+ቅድስት አትናስያም ከክርስቲያን ወላጆች ተወልዳ: እንደሚገባ አድጋ: ገና በወጣትነቷ ሁለቱም ወላጆቿ ሞቱባት:: ነገር ግን ብዙ ሃብት ትተውላታልና ምን እንደምታደርገው ሃሳብ ሆናት:: #መንፈስ_ቅዱስ ግን መልካሙን ሕሊና አደላትና አብርሃማዊ ሥራን ለመሥራት ቆረጠች::
+መጀመሪያ አገልጋዮችን አዘጋጀች:: እንደየ ወገኑ ለእንግዶችና ለነዳያን ቤትን ሠራች:: በጐውን እድል መርጣለችና ለብዙ ዓመታት ለነዳያን በማድላት: እንግዶችን በመቀበል ተጠመደች:: በዚህ ሥራዋም እግዚአብሔርንም ሰውንም ደስ አሰኘች::
+ግብሯ እንዲህ ነው:: በሌሊት ጸሎት: በመዓልት ግን እንግዶችን መቀበል: እግር ማጠብ: ማስትናገድ: ማስተኛት: ስንቅ አሰንቆ መስደድ ነው:: በዚህ ግብሯ ከምንም በላይ የወቅቱን ጻድቃን አስደስታለች::
+በዚያው ልክ ግን ዲያብሎስ ተቆጥቶ ይከተላት ጀመር:: በብዙ ጐዳና አልሳካልህ ቢለውም በክፉ ጐረቤቶቿ አማካኝነት ግን ተሳካለት:: የአካባቢዋ ሰወች ወደ እርሷ ተሰብስበው በብዙ ማታለል ከቅድስና ሕይወቷ ፈቀቅ እንድትል አደረጉ::
+እነርሱ መልካም ሥራዋን ያስተዋት በመልክ ቆንጆ ነበረችና ይህንን ተጠቅመው ነው:: "ውበትና ሀብትሽን አታባክኚ" ብለው ከጐዳና አስወጧት:: መጽሐፍ ክፉ ባልንጀርነትን የሚቃወመው ለዛ ነው:: መልካም #ክርስቲያን ማለት ባልንጀራውን የሚመርጥ ነው::
+የሚገርመው ያን ያህል እንግዳ ተቀብላበት ያላለቀ ገንዘብ አሁን ግን ተመናመነ:: ክፉዎቹ ምክራቸውን ቀጠሉ:: አካሏን እንድትሸጥ አሳምነው ሴተኛ አዳሪ አደረጉዋት:: ባንዴ ከዚያ የቅድስና ከፍታ ወርዳ አካሏን ለዝሙት የምትሸጥ ሆነች::
+ነገሩን የሰሙ ገዳማውያን ሁሉ አዘኑ: አለቀሱላት:: ይልቁኑ ለእነሱ የእናት ያህል ደግ ነበረችና ከዲያብሎስ ሴራ ሊታደጉዋት ቆረጡ:: ከመካከላቸውም #ቅዱስ_ዮሐንስ_ሐጺርን ለዚህ ተግባር መረጡ:: እርሱ በአጋንንት ላይ ስልጣን ያለው ሰው ነውና::
+እነርሱ ሱባ ይዘውላት አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ ከተማ ሔደ: ወደ ቤቷም ደረሰ:: ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር:: አባ ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ::
"እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት . . . በሞት ጥላ ሥር እንኩዋ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነሕና ክፉን አልፈራም" እያለ ቀረባት:: (መዝ. 22)
+ፈጠን ብሎ ከጐኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ:: አትናስያ ደንግጣ "ምነው?" አለችው:: "የአጋንንት ሠራዊት በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው" አላት:: አስከትሎም አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች::
+ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን አቃታት:: ተስፋም ቆረጠች:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን "ግዴለሽም: ንስሃ ግቢ:: ፈጣሪ ይምርሻል" ብሎ አሳመናት:: "እሺ አባቴ" ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ: ጫማ ሳትጫማ: ሌላ ልብስ ሳትደርብ: ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች::
+ቤቷን አልዘጋችም:: ዘወር ብላ ወደ ሁዋላም አልተመለከተችም:: ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በርሃ ሆነ:: ያ በእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት: ብርድና ፀሐይ ጐበኘው:: ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና "እረፊ" ብሏት ሊጸልይ ፈቀቅ አለ::
+መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ #መላእክት ከሰማይ የብርሃን ዓምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ:: "የማን ነፍስ ትሆን" ብሎ ወደ #አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት:: ቅዱሱም "ጌታ ሆይ! ምነው ለንስሃ እንኩዋ ብታበቃት?" ብሎ አለቀሰ::
+ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ:- "ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው ይቅር ያልኩዋትና ደስ ይበላችሁ" አለው:: ይህንን የአምላክ ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው:: "ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና: 7 ጊዜ ይነሳል::"
+"+ #ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ ድንግል +"+
=>ይህቺ ቅድስት እናት የ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሰው ስትሆን ወደ ምናኔው የገባችው ገና በ6 ዓመቷ ነው:: አባቷ ገና በልጅነቷ የሞተባት ኢዮዸራቅስያ ከእናቷ ጋር ለሥራ ወደ ግብፅ ገዳማት ይሔዳሉ:: በዚያ #ደናግል ጌታችንና እመቤታችንን ሲያገለግሉ ተመልክታ ተደነቀች::
+ምክንያቱን ብትጠይቃቸው ስለ ሰማያዊ ተስፋ ነገሯት:: የሰማችው ነገር ቢመስጣት እዚያው ገዳም ውስጥ መኖርን መረጠች:: እናት ሥራቸውን ሲጨርሱ "እንሂድ" ብትላትም ያቺ የ6 ዓመት ብላቴና "እኔ ከእንግዲህ የክርስቶስና የድንግል እናቱ ንብረት ነኝና የትም አልሔድም" አለቻት::
+እናት የሕጻን ልጇን ነገር ሰምታ "ልጄ! አንቺ ያልፈለግሺው ዓለም ለእኔስ ምን ይሰራልኛል?" ብላ እርሷም እንደ ልጇ ገዳሙ ውስጥ ቀረች:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላም እናት ታማ ዐረፈች:: ቅድስት ኢዮዸራቅስያም ንጹሕ ተጋድሎዋን ቀጠለች::
+ትዕግስት: ትሕትና: ፍቅር: ደግነትና ታዛዥነት በእርሷ ሕይወት ላይ በዝተው መገለጥ ያዙ:: እህል የምትቀምሰው በ7 ቀን አንዴ ብቻ ሆነ:: ለጸሎት ስትቆምም እስከ 40 ቀናት በተመስጦ ትቆይ ነበር:: ያቺ ብላቴና ሰይጣንን ከነ ሠራዊቱ አሳፍራዋለችና ታገላት::
+በዱላና በመጥረቢያ ሳይቀር ይመታት ነበር:: እርሷ ግን ታገሰችው:: እጅግ ብዙ ድውያንን ከመፈወስ ደርሳ ድንቅ ተአምራትን ሠራች:: በዚህች ቀንም ዐርፋ ለክብረ መንግስቱ በቃች:: ድንግል #ኢዮዸራቅስያ ለገዳሙ ሞገስ ነበረችና በዕረፍቷ ታላቅ ሐዘን ተደረገ::
=>የቅዱሳት አንስት አምላክ ከንጽሕናቸው: ትጋታቸውና ማስተዋላቸው በረከትን ይክፈለን::
=>ነሐሴ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት አትናስያ ቡርክት
2.ቅድስት ኢዮዸራቅስያ ድንግል
3.ቅዱስ ዴሚና ሰማዕት
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
7.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
=>+"+ ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ:: +"+ (1ጢሞ. 1:15)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✝🌻††† እንኳን ለቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† ✝✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!✝✝ †††
††† ✝✝ቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም✝✝ †††
††† ቸር #እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ጸጋ አንዱ #ጾም ነው:: የሰው ልጅ ከፈጣሪው ክብር እንዲደረግለት ክፋትን መስራት የለበትም:: መልካም መሆንም ይጠበቅበታል:: ለዚህ ምንጮቹ ደግሞ ጾም: ጸሎትና ስግደት ናቸው:: ያለ እነዚህ ምግባራት መቼም ወደ #ጽድቅ መድረስ አይቻልም::
ይቅርና እኛ ክፉዎቹ የሰማይና የምድር ፈጣሪ: የክብር ሁሉ ባለቤት ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደ ጊዜ የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው ጾምን ነው:: ስለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን 7 አጽዋማትን በጉባዔ ሠርታ: በአዋጅ እንዲጾሙ ታደርጋለች:: ከእነዚህም አንዱ ጾመ ፍልሠታ ነው::
"ፈለሠ" - ሔደ: ተጉዋዘ እንደ ማለት ሲሆን " #ፍልሠታ" ማለት የእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምን የዕርገት ጉዞ የሚያዘክር ቃል ነው:: #እመ_ብርሃን በዚህ ዓለም ለ64 ዓመታት ኑራ ካረፈች በሁዋላ ሥጋዋ እንደ እኛ አልፈረሰም::
ለጊዜው በዕጸ ሕይወት ሥር ቆይታ እንደ ልጇ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: እርሷ በሁሉ ነገሯ ቀዳሚና መሪ ናትና:: ጾመ ፍልሠታን የጀመሩት አበው #ሐዋርያት ሲሆኑ እንድትጾምም ሥርዓት የሠሩ ራሳቸው ናቸው:: ከ7ቱ አጽዋማትም እጅግ ተወዳጅና እየተናፈቀች የምትፈጸም ናት::
ካህናትና ምዕመናንም ጾሟን እንደየአቅማቸው ክብር በሚያሰጥ መንገድ ይፈጽሟታል::
*የቻሉ ወደ ገዳማት ሔደው ጥሬ እየቆረጠሙ: ውሃ እየተጐነጩ ክብርን ያገኛሉ::
*ሌሎቹ ደግሞ ባሉበት ደብር አካባቢ እያደሩ ሌሊት ሰዓታቱን: በነግህ ኪዳኑንና ውዳሴ ማርያም ትርጉዋሜውን: በሰርክ ደግሞ ቅዳሴውን ይሳተፋሉ::
*የኔ ብጤ ደካማ ደግሞ ጠዋት ማታ ወደ ደጇ እየተመላለሰ "አደራሽን ድንግል" ይላታል::
†††✝✝ በእርሷ አምነን አፍረን አናውቅምና ነጋ መሸ ሳንል እንማጸናታለን::
††† #ጽንዕት_በድንግልና: #ሥርጉት_በቅድስና #እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ልበለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን:: <3
*ጾሙን የፍሬ: የትሩፋትና የበረከት ያድርግልን::*
††† ✝✝ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ✝✝ †††
††† እጅግ የተወደዱ: ሞገስ የሞላላቸውና ፈጣሪያቸውን በክብር ገንዘው የቀበሩ አባቶች ናቸው::
††† ቅዱስ ዮሴፍ ዘአርማትያስ †††
††† ቅዱሱ በእሥራኤል ምድር ተወልዶ ያደገ: ኦሪትን የተማረ ባለጠጋ ሰው ነው:: የተማረ ደግ ሰው ነውና የክርስቶስን መምጣት በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: ባገኘውም ጊዜ በአዳኝነቱ (በመሲህነቱ) አምኖ በስውር ተከታዩ ነበር::
†††✝✝ ቅዱስ ኒቆዲሞስ ✝✝†††
††† ወንጌል እንደሚነግረን ይህ ሰው የአይሁድ አለቃ: መምሕር: ዳኛ እና ሃብታም ሰው ነበር:: እነዚህ ሁሉ ማነቆዎች ግን እርሱን ከፈጣሪው ሊያስቀሩት አልቻሉም:: ሌሊት እየመጣ ከጌታችን እግር ይማር ዘንድም አድሎታል:: በመካከልም ከአይሁድ ጋር ብዙ ተጋጭቷል::
ሁለቱ አባቶች መድኃኒታችን ስለ እኛ ሲል ሞቶ ባለበት ሰዓት ላይ በእርሱ የደረሰ ይደርስብናል ሳይሉ በድፍረት ሥጋውን ከዺላጦስ ተካሠው ለመኑ:: እንባቸው በፊታቸው እየወረደ ከመስቀል አውርደው በዮሴፍ በፍታና በኒቆዲሞስ ሽቱ ገነዙት::
እንዲህ እያሉ:-
"ሙታንን የምታስነሳ ጌታ አንተ ሞትክን?! ደካሞችን የምታጸና ቸር አንተ ደከምክን?!"
*በዚያች ሰዓት ጐልጐታ አካባቢ ዝማሬ መላእክትን እየሰሙ የክብር ባለቤትን ቀብረውታል:: ጌታችንም ከተነሳ በሁዋላ በንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::
"እየሳማችሁ አክብራችሁ እንደ ገነዛችሁኝ እኔም በሰማይ በእንቁ ዙፋን ላይ አስቀምጣቹሃለሁ" ብሏቸዋል:: "አነ አብረክሙ ዲበ መንበረ ሶፎር" እንዲል:: ጻድቃን አበው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በተረፈ ዘመናቸው ወንጌልን ሰብከው: ከአይሁድ መከራን ታግሰው: በበጐ ሽምግልና ዐርፈዋል::
††† ✝✝ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት✝✝ †††
††† ቅዱስ አቦሊ የሰማዕታቱ #ቅዱስ_ዮስጦስና #ቅድስት_ታውክልያ ልጅ ሲሆን በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ያበራ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ሰማዕት ነው:: የሚገርመኝ ሦስቱ የግማሹ ዓለም አስተዳዳሪዎች ነበሩ:: ዮስጦስ ንጉሥ: ታውክልያ ንግሥት: አቦሊ ደግሞ ልዑል ነው::
ነገር ግን ይህንን ክብራቸውን #በክርስቶስ ፍቅር ጐን: ሚዛን ላይ ቢያኖሩት በጣም ቀሎ ታያቸው:: 3ቱም ከዙፋናቸው ወርደው: ወገባቸውንም ታጥቀው: ባሮቻቸው በነበሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ብዙ ተንገላቱ:: መራራ ሞትንም ታገሱ::
በተለይ ቅዱስ አቦሊ ከአንጾኪያ ወደ ግብጽ (ብስጣ) ይዘው አምጥተው ክርስትናውን እንዲተው ያላደረጉት የለም:: በቁሙ ቆዳውን ገፈው: በቆዳው አቅማዳ ሰፍተው: ያንንም አሸክመው: የተገፈፈ አካሉን ጨውና ኮምጣጤ እየቀቡ አዙረውታል::
እርሱ ግን ጌታ በላከለት ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ረዳትነት ሁሉን ችሎታል:: በዘመኑ ብዙ ተአምራትን የሠራ ሲሆን አንድ ጊዜ ቤት ተንዶ 16 ሰዎች ቢያልቁ የተገፈፈ ቆዳውን እየጣለባቸው ተነስተዋል:: በተአምራቱና በተጋድሎውም ብዙ ሺህ አሕዛብን ለክርስትና: ብሎም ለሰማዕትነት አብቅቷል::
እርሱም ከብዙ የመከራ ጊዜያት በሁዋላ በዚህች ቀን አንገቱን ተከልሏል:: ጌታችን "ዜናሕን የጻፈውን: ያነበበውንና የሰማውን ይቅር እለዋለሁ" ብሎ ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል::
††† ፈጣሪ ከጻድቃንና ሰማዕታት በረከትን አይለይብን:: ወርሐ ነሐሴንም ለበረከት ይቀድስልን::
††† ነሐሴ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በአተ ጾመ ፍልሠታ
2.አበው ሐዋርያት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
3.ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት
4.ታላቁ ቅዱስ ዸላሞን ገዳማዊ
5.ቅድስት ሐና (የእመ ብርሃን እናት)
6.ቅድስት ሐና ነቢይት (ወለተ ፋኑኤል)
7.ደናግል ቅዱሳት (የንግስት ሶፍያ ልጆች)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
††† "የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ #ዮሴፍ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ዺላጦስን ለመነ:: ዺላጦስም ፈቀደለት:: ስለዚህም መጥቶ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ወሰደ:: ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ #ጌታ_ኢየሱስ መጥቶ የነበረ #ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ:: የጌታ ኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት::" †††
(ዮሐ. 19:38)
††† "በጽዮን መለከትን ንፉ:: ጾምንም ቀድሱ:: ጉባዔውንም አውጁ:: ሕዝቡንም አከማቹ:: ማሕበሩንም ቀድሱ:: ሽማግሌዎችንም ሰብስቡ:: ሕጻናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ:: ሙሽራው ከእልፍኙ: ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ::" †††
(ኢዩ. 2:15)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
❤እንኳን አደረሳችሁ ❤
#ጾመ ፍልሰታ( የእመቤታችን ጾም)
#ፍልሰታ_ማለት፡ ፈለሰ የሚል የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን መለየት ፣መሞት ማረግ ፣ወደ ላይ መውጣት ማለት ነው።
🔹ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ይላሉ አባቶቻችን ሲናገ ሩነገሩ እንደምን ነው ቢሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጥር 21ቀን ሞታ በነሐሴ 14ቀን ተቀብራለች።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደች በሗላ ከእናት አባቷ ቤት ለሶስት አመት ከ ሰባት ወር ሲሆናት ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዷት ለምን በስዕለት የተገኘች ስለሆነች ቤተ መቅደስ 12 አመት ከቆየች በሗላ ዮሴፍ ቤት በእጮኝነት እየጠበቃት ሰላሳ አራት ዓመት ከ አምስት ወር ተቀመጠች በመላኩ በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት አንች ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ የማህፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው ድንግል ማርያምም እንዲህ ያለ ሰላምታ እሱም እንዲህ አላት ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙም አማኑኤል ይባላል (ሉቃ፩፥፪፰)
🔵ክርስቶስን ወለደች እሱም ስለ አለም መከራን ቀመሰ በመስቀል ላይ ሆኖ በገዛ ፍቃዱ ክብር ነፍሱን ቅዱስ ስጋውን ከመለየቱ በፊት ለቅዱስ ዮሐንስ እነኦት እናትህ በማለት ሰጠው እሷንም እነኦ ልጅሽ አላት (ዩሐ፩፱፥፪፮) እስራ አራት ዓመት ከቅዱስ ዩሐንስ ቤት ከተቀመጠች በሗላ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በስልሳ አራት አመቷ አረፈች ሐዋርያትም የእመቤታችንን አስከሬን ለመቅበር ወደ ጌቴ ሲማኒ ሲሄዱ አይሁድ ልጇ ተነሳ አረገ እያሉ ክርስቲያኖች ሲያውኩት ይኖራሉ አሁን ደግሞ እናቱ ተነሳች እንዳይሉ አስከሬኗን እናቃጥል በማለት ተመካከሩ ከእነሱም መካከል ታውፋኒያ የተባለው ቀድሞ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዘው እጁ ዛለ ወዲያው እመቤታችን እጁን አዳነችለት ወዲያው መላዕኩም ነፅቆ በገነት አኑሮዋታል በ8 ወር በሐምሌ ሐዋርያትም አስከሬኗን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በፆሎትና በምህላ ቀብረዋታል
🔹ቅዱስ ቶማስ ከሐገር ስብከት በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ስታርግ ያገኛታል ትንሳኤሽን ሌሎች ሃዋርያት አይተው ለእሱ የቀረበት መስሎት ተናዶ በፌት የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረው አሁን ደግሞ የአንችን ትንሳኤ ሳላይ ቀርቸ ነበር ብሎ አላት።በዚህ ግዜ እመቤታችን ቶማስን አረጋጋችሁ ከእሱ በቀር ትንሳኤዋን እንዳላየ ነገረችው ቶማስም ሐዋርያት ወዳሉበት ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ግዜ እመባታችንን ቀብረናታል ብለው ነገሩት እሱም አውቆ ሚስጢሩን ደብቆ አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር አላቸው። ለማሳየትም መቃብርን ሲከፍቱ አጧት በዚህ ግዜ እመቤታችን አርጋለች አላቸው የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው ሰበኗንም ተከፋፍለው ወደ ሀገረ ስብከት ተበታትነዋል።
🔹በአመቱም ትንሳኤሽን ቶማስ አይቶ እንዴት እኛ ይቀርብናል ብለው ከ ነሐሴ ፩ ጀምረው ሱባኤ ገቡ በ ፲፬ኛው ቀን የእመቤታችንን ትኩስ በድን አምጥቶ ሰጥቷቸው አልቀበሯትም ነገር ግን በዚያ ሱባኤያቸው በ፲፮ኛው ቀን ጌታችን ሐዋርያትን ወደ ሰማይ አሳርጎ እመቤታችንን መንበሩ አድርጎ አቅርቦ ትንሳኤዋን አረጋግጦላቸዋል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክብር ይቆየን አሜን
ድንግል ሆይ ቅድስት ሆይ የአስራት ሀገርሽ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ትጠብቂልን ዘንድ ለተወደደው ልጅሽ አሳስቢልን ❤
✞✞✞✞✞ሰናይ ሚዲያ✞✞✞✞✞
>ሐምሌ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ዻውሎስ መናኒ (ከቤተሰቡ ጋር)
3.ቅዱስ ሱርያል (እሥራልዩ) ሊቀ መላእክት
4.ቅዱሳን መርቆሬዎስና ኤፍሬም (ሰማዕታት)
5.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት (ፍልሠቱ)
6.እናታችን ማርያም ክብራ ኢትዮዽያዊት (የዐፄ ናዖድ ሚስት)=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
እውነት እላችኋለሁ ሴቶች ከወለዱአቸው መካከል
ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም አልተነሣም በእግዚአብሔር መንግሥት ግን የሚያንሰው ይበልጠዋል ።
ሉቃ ፯÷፳፰(7÷28)
እንኳን አደርሳችሁ አደርሰን
ለመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
ረድኤት በረከት ይደርብን አሜን
✝ ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምሕረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡
ከአባታች ከእጨጌ አቡነ ዮሐንስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸውም ይማረን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ።
ውድ የመዓዛ ሃይማኖት የቴሌግራም ተከታታዮቻችን መዓዛ ሃይማኖት በተለያዩ መንፈሳዊ ትምሕርቶች ስናስተላልፍ መቆየታችን ይታወቃል አሁንም በማሰስተላለፍ ላይ እንገኛለን ሆኖም ግን በእናንተው በመጣልን አስተያየትና በያዝነው ዕቅድ መሰረት መዓዛ ሃይማኖት ዩቲዩብ ቻናል ላይክ ሸር በማድረግ ከመዓዛ ሃይማኖት ጋር እንዲሆኑ በአክብሮት እንጠይቃለን
እግዚአብሔር ያክብርልን፡፡
https://m.youtube.com/channel/UCKGh-U7U7pnvFUIEGXPOnNw
ነሐሴ 7/2015 #ቅድስት_ሥላሴ
👉አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለአጋእዝተ አለም ቅድስት #ሥላሴ ወርሐዊ መታሠቢያ በአል እንኳን አደረሰን
👉ምስጢረ ሥላሴ፦ ስለ ሥላሴ ምስጢር የሚናገር ትምህርት ማለት ነው እግዚአብሔር አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፋፍለው በአንድነትና በሦስትነት የሚመሰገን አንድ ሕያው አምላክ ነው
👉የእግዚአብሔር ሦስትነት ስንል፦ እግዚአብሔር የማይለያይና የማይቀላቀል ፍጹም የሆነ ሦስትነት አለው ማለታችን ነው የእግዚአብሔር ሦስትነት በስም በግብር በአካል ነው
👉እግዚአብሔር በስም ሦስት ነው ስንል ሦስት የተለያዩ ስሞች አሉት ማለታችን ነው እነዚህም፦ አብ፣ወልድ፣መንፈስ ቅዱስ የሚባሉት ሲሆኑ እርስ በርሳቸው አይወራረሱም አንዱ በሌላው ስም አይጠራም " ዘፍጥረት1፣2 " " ምሳሌ 30፣4 "
👉እግዚአብሔር በግብር ሦስት ነው፦ ስንል ሦስት የተለያዩ የአካል ሥራዎች አሉት ማለት ነው እነሱም፦ "መውለድና ፤ማስረጽ የአብ" "መወለድ፣የወልድ " "መስረጽ፣የመንፈስ ቅዱስ" የሚሉት ሲሆኑ የአካል ግብር ይባላሉ " መዝሙር 2፣7 "
👉እግዚአብሔር በአካል ሦስት ነው ማለት ደግሞ
ለአብ፤ ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው።
👉ለወልድ፤ ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው ።
👉ለመንፈስቅዱስ፤ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው ማለታችን ነው።
👉የሦስቱ የእግዚአብሔር ስሞች ትርጉም
👉አብ፦ ማለት አባት ማለት ሲሆን የሚወልድ፤የሚያሰርጽ ወይም የሚያስገኝ ያለ እናት ወልድን የወለደ፤ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ ነው።
👉 ወልድ፦ ልጅ ማለት ሲሆን የሚወለድ ወይም ያለ እናት ቅድመ ዓለም፤ ያለ አባት ድህረ ዓለም የተወለደ ነው"መዝሙር 2፣7"
👉መንፈስቅዱስ፦ ረቂቅ፤ ልዩ፤ ንፁህ; ከፍጡራን መናፍስት ሁሉ የተለየ ማለት ነው። "ኢዮብ 26፣13"
👉አለምን ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጡ " አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ #ሥላሴ ህይወታችንን በምህረት ቤታችንን በበረከት ይጎብኙልን ይባርክልን "አሜን"
👉የተባረከ የተቀደሠ #ሰንበተ_ክርስቲያን ይሁንልን ሁሉን የሚገዙ #ሥላሴ የእናታችን ማርያምን ረድኤትና በረከት ያሣድሩብን "አሜን"
"መላእክት በሰማያት እኅትነ ይብልዋ ፤ ሰማዕት ይኤምኅዋ እኅትነ ይብልዋ ፤ ጻድቃን በበነገዶሙ ይኤምኅዋ ፤ በሩካቤ ዘበሕግ እለ ወለድዋ እምቤተ ክህነት ወመንግሥት ዘኀረይዋ ፤ ይእቲኬ ማርያም ይእቲ" ቅዱስ ያሬድ
ነሐሴ ፯ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም
እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ !
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ !
††† እንኩዋን ለጻድቃን ቅዱሳን #አባ_አብርሃም: #ቅዱስ_ዮሐንስ እና #አባ_ፊልዾስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††
††† #አባ_አብርሃም_ክቡር ገዳማዊ †††
=>ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆን በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ከተነሱ ከዋክብት አንዱ ነው:: #ክርስቲያን ወላጆቹ በሥርዓት አሳድገው "ሚስት አግባ" አሉት:: እሺ እንዳይላቸው ከልጅነቱ ጀምሮ የተመኘው ምናኔ ሊቀርበት ሆነ:: እንቢ እንዳይላቸው ደግሞ ወላጆቹ ያዝናሉና የልቡን በልቡ ይዞ "እሺ" አላቸው::
+ሠርግ ተደግሶ: #ተክሊል ተደርሶ: ከአንዲት ክርስቲያን ጋር አጋቡት:: በጋብቻው ማግስት ግን ከነ ድንግልናው ጠፍቶ በርሃ ገባ:: በዚያም አንዲት በዓት አዘጋጅቶ ፈቃደ ሥጋውን እየቀጣ: ፈቃደ ነፍሱን እያለመለመ ለ10 ዓመታት ተቀመጠ::
+በነዚያ ሁሉ ዘመናት የሞቀ አልለበሰም: የላመ የጣመ ነገር አልበላም:: የፀሐይ ብርሃን እንኩዋ አልተመለከተም:: በዚያ ወራትም ወሬ ነጋሪ ወደ በዓቱ መጥቶ "ወላጆችህ ዐረፉ:: በቤት ውስጥ ከ6 ዓመት እህትህ ከማርያ በቀር ማንም የለምና የወላጆችህን ሃብት ውረስ" አለው::
+አባ አብርሃም የሚያደርገውን ያውቃልና ከበርሃ ወጥቶ ወደ ሃገር ቤት ሔደ:: ትንሽ እህቱን (6 ዓመቷ ነበር) ለቤተ ዘመድ አደራ ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን አንድ ሳያስቀር ለነዳያን በትኖ:ወደ በዓቱ ተመለሰ:: በዚያም እንዳስለመደ በጾምና ጸሎት ተወስኖ ለ10 ዓመታት ቆየ::
+ተጋድሎ በጀመረ በ20 ዓመቱ #እግዚአብሔር ለሌላ አገልግሎት ጠራው:: የግብጽ ሊቀ ዻዻስ #አባ_አብርሃምን አስመጥቶ ቅስናን ሾመውና "ሒደህ ወንጌልን ስበክ" አለው:: ችግሩ እርሱ የተላከባት ሃገር አንድም ክርስቲያን የሌለባት ከመሆኗ በባሰ እጅግ ጨካኝ ናቸው::
+ማንም ደፍሮ በዚያ ሃገር ውስጥ ነገረ እግዚአብሔርን የሚናገር ሰው አልነበረም:: አባ #አብርሃም ወደ ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው እንደ ልማዳቸው መሬት ላይ ጥለው ደበደቡት: አጥንቶቹንም ሰባበሩት:: ሞቷል ብለው ከከተማ ውጪም ጣሉት::
+እርሱ ግን በፈጣሪው ኃይል ጸንቶ ተነሳ:: ማስተማሩ ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን ተረድቷልና ስለ እነሱ ተግቶ ይጸልይ ጀመር:: አሕዛብ ጠዋት ቢመጡ በከተማዋ መሐል ላይ ሲጸልይ አገኙት:: ስለ ተናደዱ ድጋሚ አካሉን በዱላ ሰባብረው እየጐተቱ ከከተማ አስወጡት:: በዚያም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት::
+ነገር ግን ጠዋት ሲመለሱ እዛችው ቦታ ላይ ሲጸልይ አገኙት:: ይሕ የሚደረገው ለእነርሱ ድኅነት መሆኑን አልተረዱምና እነርሱ በየቀኑ እየደበደቡና እያሰቃዩት እርሱ ስለ እነሱ እየጸለየ 10 ዓመታት አለፉ:: ቅዱሳን ተስፋ አይቆርጡምና በመጨረሻው ተሳካለት::
+የቅዱሱ የዘመናት ጸሎት ፍሬ አፍርቶ እግዚአብሔር በአሕዛብ ልቡና ያደሩ አጋንንትን አራቀለት:: አንድ ቀን ጠዋት የሃገሩ ሕዝብ ሁሉ (ወንዱ: ሴቱ: ትልቁ: ትንሹ) ወደ ጻድቁ መጸለያ መጡ:: ለእርሱስ የጠብ መስሎት ነበር:: እነርሱ ግን በአንድነት በፊቱ ተንበርክከው ሰገዱ:: ይቅር እንዲላቸውም ለመኑት::
+ቅዱሱ ይሕንን ሲመለከት ሐሴትን አደረገ:: ሁሉንም #በስመ_ሥላሴ አጥምቆ ክርስቲያን አደረጋቸው:: አብያተ ክርስቲያናትንም አነጸላቸው:: በሁዋላ ግን በጣም ሲወዱትና ሲያከብሩት ተመልክቷልና ከውዳሴ ከንቱ (#ስብሐት_ብጡል) መለየት ፈለገ:: ፈጣሪንም በቸርነቱ እንዲጠብቃቸው ለምኖ: በሌሊት ጠፍቶ ወደ ነበረበት በርሃ ገባ::
+እርሱ በበርሃ ሁኖ ስለ ትንሽ እህቱ #ማርያ ያስብ ነበርና አስጠራት:: "ምን ትፈልጊያለሽ?" አላት:: እርሷም "እንዳንተ መሆን" ስላለችው አስተምሮ: ፈትኖ አመነኮሳት:: ለጥቂት ዓመታት በሥርዓት ከኖረች በሁዋላ ግን ችግር ተፈጠረ::
+ከአንድ መነኩሴ ጋር በነበራት ያልተገባ ቅርርብ የዝሙት ፍላጐታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በኃጢአት ወደቁ:: በዚህ ተስፋ ቆርጠው 2ቱም ቆባቸውን ጥለው ከተማ ገቡ:: ይልቁኑ እርሷ (ማርያ) ሴተኛ አዳሪ ሆነች::
+በዚያ ሰሞን ቅዱሱ አብርሃም ራዕይን ያያል:: ትልቅ ዘንዶ አንዲት ርግብን ሲውጣት: መልሶም ሲተፋት አይቶ እሕቱ መሆኗን ተረዳ:: ወዲያው ጥሩ ልብስና ፈረስ ተውሶ ተነሳና ወደ ከተማ ገባ:: የጦር መኮንን መስሎ እህቱ ቤት ገባ::
+ሸሽታ እንዳታመልጠው ቤቱን ዘጋና ራሱን ገለጠላት:: ደንግጣ እንደ በድን ብትሆንም እርሱ አረጋጋት:: "እህቴ! ንስሃ ግቢ: አምላክ ይራራልሻል" አላት:: ልቧ ወደ ምክሩ አዘንብሏልና የእህቱን ነፍስ ማርኮ ወደ ገዳም ተመለሰ::
+በዚያ በዓት ሠርቶላት: ቀኖናም ሰጥቷት ሔደ:: #ማርያም ስለ ኃጢአቷ ፈንታ የምትገርም የቅድስና ሰው ሆነች:: ያየ ሁሉ እየተደነቀባት ከዓመታት ተጋድሎ በሁዋላ ዐረፈች:: አባ አብርሃም በተረፈ ዘመኑ በንጹሕ ገዳማዊ ሕይወት ተጠምዶ ኑሯል::
+በዘመኑ ሁሉ በጥርሱ ስቆ: በከንፈሩም አልባሌ ነገርን ተናግሮ አያውቅም:: ልቡ በፈጣሪው ፍቅር የታሠረ ነበርና ሕማማተ ክርስቶስን እያሰበ እንባው ያለማቁዋረጥ ይፈስ ነበር:: ደግና ቅዱስ ሰው አብርሃም በዚህች ቀን ዐርፎ ተቀብሯል::
††† #ቅዱስ_ዮሐንስ_ጻድቅ †††
=>ይህ ቅዱስ የነበረው በዘመነ ሰማዕታት ቢሆንም እንደ ሰማዕታት ስቃይ አልደረሰበትም:: ክርስቲያኖችን እንዲገድሉና አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያቃጥሉ ከተመደቡ ወታደሮች አንዱ ነበረ:: ታዲያ እንዲገድላቸው የሚሰጡትን ክርስቲያኖች እየወሰደ ይደብቃቸው ነበር::
+የመከራው ዘመን እስኪያልፍ ድረስም ይንከባከባቸው ነበር:: ሌሎች ወታደሮች እንዳይነቁበት ሁሌም "ክርስቲያኖችን በጣም እጠላለሁ" እያለ ያወራ ነበር:: እርሱ በሌሊት ሁሌም ለጸሎት ይተጋ ነበር:: በእንዲህ ያለ ግብር ኑሮም በዚህች ቀን በሰላም ዐርፏል::
††† #አባ_ፊልዾስ #ዘደብረ_ቢዘን †††
=>#ደብረ_ቢዘን በቀድሞ የኢትዮዽያ ክፍለ ሃገር (አሁን #ኤርትራ) ውስጥ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው:: ገዳሙ #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም በስደቷ ያረፈችበት: ጌታችን የባረከውና የመረጠው ቦታ ነው:: #አባ_ዮሐንስን: #አባ_ናርዶስንና ሌሎች ከዋክብት አበውን ያፈራ ሲሆን የአባ ፊልዾስን ያሕል ግን አልተገኘም::
+ጻድቁ በግል የተጋድሎ ሕይወታቸው: ገዳሙን በአበ ምኔትነት በመምራታቸውና በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ምስጉን ነበሩ:: እርሳቸው ቅዱስ ሆነው አልበቃቸውምና ብዙ ቅዱሳንን ወልደዋል:: ይሕች ዕለትም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ናት::
=>አምላከ ጻድቃን ገዳማትን ከመከራ ይጠብቅልን:: ከአባቶቻችን ቅዱሳን ጸጋ በረከትንም ይክፈለን::
=>ነሐሴ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ አብርሃም ገዳማዊ
2.ቅድስት ማርያ እህቱ
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ
4.አባ ፊልዾስ ዘደብረ ቢዘን
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
6.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)
=>+"+ በድካም: አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ. . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው:: +"+ (2ቆሮ 11:23)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† ✝እንኳን ለጻድቅ ንጉሥ ሕዝቅያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††✝
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
†††✝ ቅዱስ ሕዝቅያስ✝ †††
††† ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን ከመድኃኒታችን ክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመታት በፊት ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር:: ደጋጉ ዳዊትና ሰሎሞን ካረፉ በኋላ የሕዝቅያስን ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም ነበር::
ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት:: ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከመቶ ሰማንያ አምስት ሺ በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::
"እገብርልሃለሁ: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ነገር ግን ሃገሬን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል: ሕዝቤንም አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::
ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ: ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ ማነው? ሕዝቡንም እግዚአብሔር ያድናል ብለህ አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::
መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ::
በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ::"
በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ:: በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::
በድንጋጤ ወደ ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖት የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)
ቅዱስ ሕዝቅያስ የነሐስ እባቡን በማጥፋቱ: ሕዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በመመለሱ ቢደነቅም ሰው ነውና አንዲት ጥፋት አጠፋ:: በዘመኑ ታላቁ ነቢይ ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ነበረና ሐረገ ትንቢትን ያፈስ ነበር:: ከተናገራቸው ትንቢቶችም አንዱ "ድንግል ትጸንሳለች: ወንድ ልጅም ትወልዳለች" የሚል ነበር:: (ኢሳ. 7:14)
በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ክፉ መካሪዎች ቀርበው ንጉሡን በውዳሴ ከንቱ ጠለፉት:: "ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ:: እንዳንተ ያለ ማንም የለም:: ነቢዩ የተናገረው ትንቢትም እኮ ላንተ ነው:: "ድንግል" የተባለች ኢየሩሳሌም ስትሆን "ወልድ-ወንድ ልጅ" የተባልክ ደግሞ አንተ ነህ" አሉት::
ይሕንን ጠማማ ትርጉም እህ ብሎ የሰማቸው ቅዱስ ሕዝቅያስ አልወቀሳቸውም:: ይልቁኑ ልቡ ወደ እነሱ አዘነበለ እንጂ:: በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ኢሳይያስን ላከው::
ነቢዩም በቀጥታ መጥቶ ንጉሡን አለው:- "ትሞታለህ እንጂ አትተርፍምና ቤትህን ሥራ::"
ወዲያውኑ ሕዝቅያስ ታመመ: ደከመ:: ነገር ግን ፊቱን ወደ ቤተ መቅደስ አዙሮ ሊያዝን: ሊተክዝም ጀመረ:: አባቶቻችን ለየት የሚያደርጋቸው ይኼ ነው:: በቅድስና ኑረው: ሰው ናቸውና ይሳሳታሉ:: ነገር ግን ንጹሕና ፍጹም ንስሐን ከማቅረብ አያቋርጡም::
ንጉሡ ቅዱስ ሕዝቅያስ ወደ ፈጣሪ:- "ጌታ ሆይ! እንደ ቸርነትህ በፊትህ በቅን መንገድ መሔዴን አስብና ይቅር በለኝ" ሲል ተማጸነ:: ይህ ሲሆን ቅዱስ ኢሳይያስ ገና ከንጉሡ አካባቢ አልራቀም ነበርና የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ::
ሕዝቅያስን በለው:- "ጸሎትህን ሰምቼ: ስለ ባለሟሌ ስለ ዳዊት ብዬ ምሬሐለሁ:: በዘመንህም ላይ አሥራ አምስት ዓመታትን ጨምሬልሃለሁ በለው" አለው:: ነቢዩም ወደ ንጉሡ ተመልሶ ይሕንኑ ነግሮ "እስከ ሦስት ቀን ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ ድነህ ትመለሳለህ" አለው::
ቅዱስ ሕዝቅያስ "ይሕ እንደሚደረግ በምን አውቃለሁ?" አለው:: (ተጠራጥሮ ግን አይደለም: ድንቅ ተአምር ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ) ኢሳይያስም ፀሐይን ዓለም እያየ አሥር መዓርጋትን ወደ ኋላ መለሳት:: በወቅቱ ይህ ተአምር በመላው ዓለም ታይቶ: ተሰምቶም ነበርና ሕዝቅያስ ከፍ ከፍ አለ::
በቅን የሔደ: እግዚአብሔርም የወደደው እንዲህ ነው:: የዓለም ነገሥታት ሁሉ ለሕዝቅያስ አዘነበሉ: ገበሩለትም:: ለእርሱ ጌታ ድንቅ ነገርን አድርጐለታልና::
ቅዱስ ሕዝቅያስ በተጨመሩለት ዘመናት ሁሉ እግዚአብሔርን አመለከ:: በፊቱም በቅን ተጓዘ:: ከክርስቶስ የዘር ሐረግም በቀጥታ ተቆጠረ:: (ማቴ.1:10) ለአሥራ አምስት ዓመታት ሕዝቡን አስተዳድሮ በዚህች ቀን እድሜ ጠግቦ ዐርፏል:: በእርሱ ዙፋን ላይም ልጁ ምናሴ ተተክቷል::
††† ✝አባ ማቴዎስ ገዳማዊ✝ †††
††† እኒህ ቅዱስ ሰው በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ፋርስ አካባቢ የነበሩ ጻድቅ ናቸው:: በወቅቱ ምንኩስና በአካባቢው ባለመስፋፋቱ ወደ ዱር እየወጡ የሚኖሩ አበው ነበሩና አባ ማቴዎስ አንዱ ናቸው:: እርሳቸው በበርሃ ልብሳቸው አልቆ አካላቸው የሚሸፈነው በጸጉራቸው ነበር::
የአቶር ንጉሥ የሰናክሬም ልጅ መርምሕናምን(እጅግ ታላቅ ሰማዕት ነው) ያሳመኑትና ያጠመቁት እርሳቸው ናቸው:: እኅቱን ሣራንም ከለምጿ አንጽተው ወደ ክርስትና መልሰዋል:: በዚህ ምክንያትም የፋርስ አውራጃ የሆነችው አቶር በሙሉ የክርስቲያኖች ቤት ሆናለች:: አባ ማቴዎስ ከዘመናት ተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፈዋል::
††† አምላከ ቅዱሳን እድሜ ለንስሐ: ዘመን ለፍስሃ አይንሳን:: የጻድቃኑ በረከትም ይደርብን::
††† ነሐሴ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሕዝቅያስ ጻድቅ (ንጉሠ ይሁዳ)
2.አባ ማቴዎስ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ዳዊት ሰማዕት
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ (ወንጌላዊው)
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)
††† "አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል::
በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል::
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው:: የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም::
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና::
ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ::
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም:: ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ::
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው::" †††
(መዝ. ፳፥፩-፭)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ደስ ያለህ ባለ ምሥራች ገብርኤል ሆይ! ወደኛ የመጣ የጌታን ልደት ነግረኸናልና ላንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ አንድም “ወነዋ ተወልደ ፍስሐ ዘይከውን ለክሙ ወለኩሉ ዓለም - እነሆ ለሕዝቡ ኹሉ የሚኾን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ” ብለህ /ሉቃ.፪፡፲/ የጌታን ልደት ለኖሎት (ለእረኞች) ነገርኻቸዋልና ለአንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ “እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ካንቺ ጋራ አንድ ይሆናልና ደስ ይበልሽ” ብለህ /ሉቃ.፩፡፴/ ለእመቤታችን
ነግረኻታልና ለአንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡
እንዲህ ካለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፬. መንፈስ ቅዱስ ቢያድርብሽ፣ ኃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ቢለብስ ጸጋን አገኘሽ፡፡ መንፈሰ ቅዱስ ከሦስቱ ግብራት ቢከለክልሽ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለው ከሚመሰገኑት ከሦስቱ አካላት አንዱን ቅዱስ ወለድሽልን፡፡ ሰውን ኹሉ የሚያድን እርሱም ሰው ኾኖ አዳነን፡፡
ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. ቀድሞ ከነበሩት ጋር አንድ ኾኖ አንደበታችን የድንግልን ሥራ ያመሰግናል፡፡ ዛሬ ካሉት ጋር ኾኖም እመቤታችንን ያመሰግናል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት አገር በዳዊት ባሕርይ ካርሷ ተወልዷልና፡፡ አሕዛብ ሆይ! ኑ እመቤታችንን እናመስግናት /ሃይ.አበ.፷፮፡፳/፡፡ እናትን ኹናለችና፤ ድንግልናም ደርባለችና ኑ እመቤታችንን እናመስግናት፡፡ አካላዊ ቃል ካንቺ ሰው የኾነ አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ድንግል ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ንጹሕ ሽቱ ዕቃ ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ የሽቱን ዕቃ ጢስ እንዳይተንበት ትቢያ እንዳይበንበት ቤት ሰፍተው፣ ሰቅለው፣ ተንከባክበው ያኖሩታል፡፡ እርሷንም “መንፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ ከመ ኢትጌጊ - እንዳትበድል ድንግልን ከእናቷ ሆድ ጀምሮ የጠበቃት መንፈስ ቅዱስ እንዳትረክስም ያነጻት ለወልድ ዋሕድም ማደርያ ያደረጋት እርሱ ነው” ይላታልና /አርጋኖን ዘእሑድ፣ ቁ.፲፰/፡፡ ዐጤ ዘርዐ ያዕቆብም በነገረ ማርያም መጽሐፉ፡- “ንጽሕት ይእቲ እምኵሉ ትሕዝብት ወእምኵሉ ርስሐተ ኀጢአት - እርሷ (እመቤታችን) ከርስሐተ ኀጢአትና ከመጠራጠርም ኹሉ ንጽሕት ናት” ብሏል /ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣ ገጽ ፶፮-፶፯/፡፡
ስለ ቀደመ ሰው (ስለ አዳም) ዳግመኛ አዳም የተባለ የክርስቶስ እናቱ ነባቢት ገነት ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከአባቱ ዕሪና (አንድነት) ያልተለየ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው እርሱን የወሰንሺው በፍጹም ጌጥ ያጌጠች ንጹሕ የሰርግ ቤት ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ የሰርግን ቤት አስቀድመው በሐር ያንቆጠቁጡል፤ ያነጽፉታል፤ ይጎዘጉዙታል፤ ሽቱ ያረበርቡበታል፤ ሐረግ ወርድ ይሥሉበታል፡፡ እንደዚህም ኹሉ አስቀድመን እንደተናገርን መንፈስ ቅዱስ ድንግልን ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጠብቋታልና እንዳትረክስም አንጽቷታልና እንዲህ አለ፡፡ አንድም በየጊዜው የጸጋ ክብር ይጨመርላታልና፡፡
ባሕርየ መለኮቱ ያልለወጠሽ ዕፀ ጳጦስ ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ (ዕፀ ጳጦስ ማለት በሀገራችን ደደሆ፣ እንጆሪ የምንለው ነው) /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም የዚህን ግሩም ምሥጢር “ዲያተሳሮን” በተባለ መጽሐፉ ሲተነትነው ፡- “ፈጣሬ ዓለማት ቅዱስ እግዚአብሔር የወደቀውን ፍጥረቱ ወርዶ ያነሣው ዘንድ፣ ቆሽሾ የነበረው ሕንፃዉንም (ሰውንም) ይወለውለው ዘንድ ተገቢ ነበር፡፡ በመኾኑም ፈጣሪ ራሱ በሰው ልጆች ላይ ፈርዶት የነበረውን ፍርድ የባሕርይ ልጁ እንዲሸከመው ካደረገ (በእርግጥም አድርጐታልና) የሰው ልጅ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ይመለሳል ማለት ነው (በርግጥም ተመልሷል)፡፡ ይህ አካላዊ ቃል፣ በሰው መተላለፍ ምክንያት በቅለው የነበሩት እሾክንና አሜኬላን ያቃጥል ዘንድ የመጣ ነባቢ ፍሕም ነው /ዘፍ.፫፡፲፰፣ ኢሳ.፱፡፲፰/፡፡ መጥቶም በማኅፀነ ድንግል አደረ፤ አነጻው፤ የጭንቅና የርግማን ቦታ የነበረው ማኅፀን ቀደሰው /ዘፍ.፫፡፲፮/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ያየው ነበልባል ሐመልማሉን አላጠፋውም፤ ይልቁንም እንዲለመልም አደረገው እንጂ /ዘጸ.፫፡፪-፫/፡፡ የነጠረ ወርቅ የሚመስል አካልም ወደ ነበልባሉ ገባ፤ ኾኖም አሁንም እሳቱ አልፈጀውም፡፡ ይኸውም በዘመኑ ፍጻሜ ሊመጣ ላለው ነባቢ እሳትና የድንግልን ማኅፀን አለምልሞ ቁጥቋጦውን እንደከደነውም እንደሚከድናት የሚያስረዳ ነው” ብሏል፡፡ ዳግመኛም አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫ የእሳተ መለኮት መምጣት ምክንያቱ ሲገልጽ፡- “… (ጌታችንም) የዓለምን ኃጢአት በትከሻው ተሸክሞ ወደ ዕፀ መስቀል ወጣ፡፡… ያን ጊዜ እግዚአብሔር እሾኽና አሜኬላ ይብቀልብህ ብሎ በረገመው ጊዜ በአዳም ሥጋ የበቀለ የኃጢአት እሾኽ ተቃጠለ” ብሏል /መጽሐፈ ምሥጢር ፲፱፡፳፩/፡፡
በኪሩቤል አድሮ የሚኖረው ሰማያዊ መለኮትን በሥጋ የተሸከምሽው ማኅደርም የተባልሽ እመቤትነትን ከገረድነት፣ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብረሽ የያዝሽ ሰማይ ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ስለዚህ ነገር፡- “አምላክ ለኾነ ለሥጋ ከሥላሴ ጋራ በአንድነት ምሥጋና ይገባዋል፤ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ” እያልን ንጹሐን ከኾኑ መላእክት ጋር በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝተን እናመስግን፡፡ ክብር የክብር ክብር ያለው እርሱ አንቺን ለእናትነት መርጧልና ንጹሐን ከኾኑ መላእክት ጋር
በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝተን እናመስግን /ሉቃ.፪፡፳/፡፡
አንቺን ለእናትነት ከመረጠ ልጅሽ ጽንዕት ሥርጉት በቅድስና በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳነሳን ለምኚልን፡፡
፮. ከቅዱሳን ክብር የእመቤታችን ክብር ይበልጣል፡፡ አካላዊ ቃልን ለመቀበል በቅታ ተገኝታለችና፡፡መላእከት የሚፈሩትን፣ ትጉሃን በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ቻለችው፡፡ እንዲህም ከኾነ ከመላእክት ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትበልጣለች፤ ከሦስቱ አካል ላንዱ ማደሪያ ኾኖለችና፡፡ ኢትዮጲያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስም ይህን በኆኅተ ብርሃን መጽሐፉ ላይ ሲገልጽ “አንቲ ተዓብዪ እምኪሩቤል ወትፈደፍዲ እምሱራፌል፣ እምሱራፌል ወኪሩቤል በሠረገላ እሳት ይጸውርዎ ወበምጽንዐ እሳት ይጼንዑ መንበሮ፤ ወአንቲሰ ጾርኪዮ በከርሥኪ ወሐዘልኪዮ በዘባንኪ ወሐቀፍኪዮ በአብራክኪ ህየንተ ሠረገላ እሳተ አብራክኪ ኮነ ወህየንተ ምጽንዐቲሁ ዘእሳተ እደውኪ ኮና - ከኪሩቤል ይልቅ አንቺ ትበልጫለሽ፤ ከሱራፌልም ይልቅ አንቺ ትልቂያለሽ፤ ኪሩቤልና ሱራፌል በእሳት ሠረገላ ተሸክመውታልና፤ አንቺ ግን በማኅፀንሽ ወሰንሺው፤ በዠርባሽም አዘልሺው፤ በጉልበቶችሽም ዐቀፍሽው፤ ጉልበቶችሽም እንደ እሳት ሠረገላ ኾኑ፤ እጆችሽም እንደ እሳት አዕማድ ኾኑ” በማለት የተሰጣት ክብር ከኪሩቤል ከሱራፌል የበለጠ መኾኑን አስተምሯል፡፡ የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ይህች ናት፡፡ መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰን ከእርሷ በነሣው ሥጋ ምክንያት ነውና ደስ ብሏቸው የሚኖሩ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት ማደሪያቸው ይህቺ ናት፡፡ በድንቁርና በቀቢፀ ተስፋ ለነበሩ ሰዎች ዕውቀት ተሰጣቸው፤ ክርስቶስ
ተወለደላቸው /ኢሳ.፱፡፪/፡፡ ወንጌል ተጻፈላቸው /ሉቃ.፩፡፩-፬/፡፡
††† እንኳን ለታላቁ አባት አባ ስምዖን ዘዓምድ እና ቅድስት ሶፍያ ቡርክት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ †††
††† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ ይህ ቅዱስ ነው:: ተወልዶ ያደገው በሶርያ (ንጽቢን) ውስጥ ሲሆን ዘመኑም 4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: አባ ስምዖን ዘዓምድ የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የልጅነትና የተማሪ ቤት ባልንጀራ ነው::
ሁለቱንም ያስተማራቸው ደግሞ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን ነው:: ቅዱሳኑ አባ ስምዖንና ቅዱስ ኤፍሬም ለአገልግሎት ከተለያዩ በኋላ አንድ ቀን ተገናኙ::
ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያምን
"እመቤቴ" እያለ ደጋግሞ በጉባኤ ሲያመሰግናት በመስማቱ "ወንድሜ! ይህን ምሥጢር ማን አስተማረህ?" አለው::
ቅዱስ ኤፍሬምም "ተገልጾልኝ ነው" እንዳይል ውዳሴ ከንቱን ፈርቶ "ቅዱስ ያዕቆብ ነው ያስተማረኝ" ቢለው በአባ ስምዖን ጠያቂነት ወደ መቃብሩ ሔደው ቅዱሱን ከሞት ቀስቅሰውታል:: እርሱም የእመቤታችንን ክብርና የቅዱስ ኤፍሬምን ጸጋ መስክሮ ዙሮ ዐርፏል::
በዚህ የተገረመው ቅዱስ ስምዖን ለቅዱስ ኤፍሬም ሰግዶለት: እመቤቴን ስንቅ ይዞ ወደ በርሃ ሔደ:: ተጋድሎን: ጾምና ጸሎትን በእረኝነት ሕይወት (በሰባት ዓመቱ) የጀመረው ቅዱስ ስምዖን በርሃ ከገባ በኋላ በእጅጉ አሳደገው:: ቅዱሱ በወገቡ የሚሻክር ገመድ አሥሮ: ምግብ ሳይበላ ዕለት ዕለት ያጠብቀው ነበር::
ከጊዜ በኋላ ገመዱ ሆዱን ቆርጦት ወደ ውስጥ ገብቶ ነበርና ሲራመድ በእግሩ ደም ጠብ ጠብ ሲል ይታይ ነበር:: ይሕንን መመልከት ጭንቅ የሆነባቸው መነኮሳት ለአበ ምኔቱ ተናግረው ቁስሉን አድነውና ገመዱን አውጥተው ከገዳም አባርረውታል::
እርሱ ግን ይህንን የሚያደርገው ሕማማተ ክርስቶስን ለመሳተፍ ነው:: ከገዳም ከተባረረ በኋላ ቅዱሱ በበርሃ ውስጥ ወደ ሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ አራዊት: እባብና ጊንጥ ከበውት ይጸልይ ነበር:: እግዚአብሔር ግን በራዕይ ለገዳሙ አበ ምኔት ተገልጾ "ወዳጄን ስምዖንን ካልመለስከው አልምርህም" አለው::
በዚህ ምክንያት መነኮሳት በጭንቅ ፈልገው አግኝተው: ከእግሩ ወድቀው ይቅርታ ጠይቀውታል:: እርሱ ግን ከመነሻውም የሚቀየም ልብ አልነበረውም:: ቅዱስ ስምዖን ወደ ገዳሙ ተመልሶ ለዘመናት በተጋድሎ ጸንቶ ቀጠለ::
እግዚአብሔር ግን ቅዱሱን ከገዳሙ ወጥቶ ወደ አንዲት ምሰሶ እንዲሔድ ስላዘዘው አሥራ አምስት ሜትር ያህል ርዝመት ባለው ምሰሶ ላይ ቆመ:: ከዚህች ቀን በኋላ ነው እንግዲህ "ስምዖን ዘዓምድ (የምሰሶው አባት)" የተባለው:: ቅዱሱ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ያለ ምንም ዕረፍት እንቅልፍ እና መቀመጥ ቆሞ
ጸልዩዋል::
ቦታዋ ለከተማ ቅርብ በመሆኗ ብዙዎችን ፈውሷል:: በእርሱ ስብከት ወደ ሃይማኖት የተመለሱ: ንስሐ የገቡ ቁጥር የላቸውም:: አንዳንዴ ክፉ ሰዎች መጥተው እርሱን በማየት ብቻ ይለወጡ ነበር:: ከቆመባቸው ዘመናት አሥራ ሁለት ዓመታት ያህልን ያሳለፈው በአንድ እግሩ ቆሞ: ሌላኛው እግር ቆስሎ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ የሰይጣን ዱላ ነበር::
ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ ከእነዚህ የተጋድሎ ዘመናት በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል:: የዕረፍቱ ዜናም ከቤተ መንግስት እስከ ቤተ ክህነት ሁሉን አስደንግጧል:: እርሱ ለመንጐቹ ዕረፍት ያልነበረው ታላቅ አባት ነበርና:: ሊቃነ ጳጳሳት ገንዘውት: መኳንንት ተሸክመውት ሥጋው በክብር ዐርፏል:: ብዙ ተአምራትም ተደርገዋል::
††† ቅድስት ሶፍያ ቡርክት †††
††† ይሕች ቅድስት እናት ኢጣሊያዊት (የአሁኗ ጣልያን አካባቢ) ስትሆን የነበረችው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው:: ትውልዷ የነገሥታቱ ዘር ውስጥ እንደ መቆጠሩ እጅግ የተከበረች ሴት ነበረች:: ምንም ሥጋዊ ክብሯ እንዲህ ከፍ ያለ ቢሆንም መንፈሳዊነቷ የሚደነቅ ነበር::
ከነገሥታቱ ዘር ካገባችው ባሏም ሦስት ሴቶች ልጆችን አፍርታለች:: በሃይማኖት ምክንያት መከራ ሲመጣ ስለ ልጆቿ ስትል ሃገሯን ጥላ ተሰደደች:: ስለ ክርስትናም በባዕድ ሃገር መጻተኛ ሆነች:: ያም ሆኖ ክፉዎቹ እግር በእግር ተከትለው ደረሱባት::
ቅድስት ሶፍያ ከዚህ በላይ መሸሸትን አልፈለገችም:: ከልጅነታቸው ለተባረኩ ልጆቿ ገድላተ ሰማዕታትን ታስጠናቸው ነበርና አሁን የነገር መከናወኛ ደርሷል:: ልጆቿን ቁጭ አድርጋ አዋየቻቸው::
"ልጆቼ! ክርስቶስን የወደደ ክብሩ በሰማይ እንጂ በምድር አይደለም:: ገድላቸውን ያነበባችሁትን ቅዱሳት አንስትን አስቡ" አለቻቸው:: ሦስቱ ሕፃናትም "እናታችን አትጨነቂ:: እኛ ለአምላክ ፍቅር ተገዝተናል:: ስለ ስሙም ደምን ልንከፍል ቆርጠናል:: ብቻ የእርሱ ቸርነት: ያንቺም ምርቃን አይለየን እንጂ" አሏት:: ቅድስት ሶፍያ በሰማችው ነገር እጅግ ደስ አላት::
ከዚያ ጉዞ ወደ ምስክርነት አደባባይ አደረጉ:: ቅድስቷ እናት ሦስቱንም ሕፃናት በመኮንኑ ፊት አቀረበች:: አንድ በአንድ ጠየቃቸው:: ሁሉም ግን መልሳቸው የተጠናና ተመሳሳይ ሆነበት:: "እኛ የክርስቶስ ነን" ነበር ያሉት:: መኮንኑ በቁጣ ሦስቱንም እያከታተለ አስገደላቸው::
ቅድስት እናት ሶፍያ በእንባ እየታጠበች ልጆቿን
በየተራ ቀበረች:: ስለ ሃይማኖቷ ክብሯን: ሃገሯን: ሃብቷን: መንግስቷን ሰጠች:: ከምንም በላይ ግን ልጆቿን ሰጠች:: ከዚህ በኋላ ግን በመጨረሻው ወደ ልጆቿ መቃብር ሒዳ በእንባ ለመነች::
"ልጆቼን አይ ዘንድ ናፍቄአለሁና ጌታ ሆይ! ውሰደኝ" አለች:: ከደቂቃዎች በኋላም እዚያው ላይ ዐረፈች:: የአካባቢው ሰዎች ደርሰው እርሷንም ከልጆቿ ጋር ቀበሯት::
††† መድኃኔ ዓለም ከታላቁ አባ ስምዖንና ከቅዱሳት አንስት በረከትን ያድለን:: ትዕግስታቸውንም ያሳድርብን::
††† ነሐሴ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ
2.ቅድስት ሶፍያ ቡርክትና ደናግል ልጆቿ
††† ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
7.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)
††† "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል:: እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል::
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል:: በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ::
ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ:: ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ::" †††
(መዝ. ፺፩፥፲፪)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
‹‹ኮከበ ክብር ጽዱል ፀሐዬ አግዓዚ ብሩህ አቡነ ጊዮርጊስ ጥዑመ ስመ ወሠናየ ግዕዝ መጋቤ ሃይማኖት ወመሠረተ ቤተ ክርስቲያን፤ አባታችን ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሚያበራ የክብር ኮከብ፣ የኢትዮጵያ ብሩህ ፀሐይ፣ ስሙ የሚጣፍጥ፣ ምግባሩ የቀና ነው።›› (ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ)
የቅዱሳን ታሪክ የትውልድን አእምሮ የሚያንጽ እንዲሁም የእነርሱን ፈለግ እንድንከተል የሚያደረግ ነው፡፡ የቀደመውን ትውልድ በማውሳት፣ አሁን ያለውንና ወደፊት የሚመጣውን ትውልድ ደግሞ ከተያዘበት የኃጢአት አረንቋ ለማውጣትና ካለበት የሥጋ ሕማም ለመፈወስ እንዲሁም ሃይማኖትንና ጥበበ እግዚአብሔር ገንዘብ አድርጎ መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርስ የደከሙት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ከቅዱሳኑ አባት አንዱ ናቸው።
አባ ጊዮርጊስ የተወለዱት ጥንተ ስሙ ብሔረ አምሃራ ነገሥታት መናገሻ ከነበረው ከአማራ ሳይንት አካበ በአሁኑ ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በቦረና አውራጃ በከለላ ወረዳ በወለቃ እናበበቶ ወንዝ መካከል በምትገኘዋ ልዩ ስሟ ሸግላ/ሰግላ/ደብረ ማኅው በ፲፫፻፶፯ ዓ.ም በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ አባታቸው ሕዝበ ጽዮን እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፤ ቤተሰቦቻቸው ከካህናት ወገን እና ከነገሥታት ወገን ናቸው። እንደነ ኤልሳቤጥ እና እንደ ዘካርያስ በሕግ የጸኑ ደጋግ አባቶች ቢሆኑም ልጅ ስለ አልነበራቸው፤ ዘወትር ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመመለስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስዕል አድኅኖ ፊት እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ይጸልዩ ነበር። ሁሉን ማድረግ የሚቻለው እግዚአብሔር ጸሎታቸዉን ካደረሱ በኋላ ‹‹አስመ አልቦ ነገር ዘይሳኖ ለእግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና›› ይህን ቅዱስ በቅዱስ ዑራኤል አብሣሪነት ተወልዷል፤ ቅዱሱ ጥቅምት ሦስት ቀን ፲፫፻፶፯ ዓም ተፀንሰው ሐምሌ ፯ ቀን ዕለተ ማክሰኞ ቅድስ አባታችን ተወለዱ። (ድርሳነ ዑራኤል)
አብርሃም ሥላሴን ባስተናገደበት ዕለት አባ ጊዮርጊስ ዕድሚያቸው ለትምህርት እስኪ በቃ ድረስ እናታቸው ጋር እግዚአብሔርን እንዲፈራና ትሕትናን ገንዘብ እንዲያደርግ እናቱ አስተማረችው። ከዚህ በመቀጠል አባታቸው በቤተ መንግሥት ከሚያገለግሉ ካህናት ወስደው ልጃቸውን በመልካም አስተዳደግ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት በማስተመር አሳደጓቸው። ምንም እንኳን አባታቸው ወደ ተምህርት ቤት ቢወስዷቸውም ትምህርት ቶሎ ሊገባቸውም አልቻለም ነበር፤ ይህ የእርሳቸው ትምህርት አለመግባት የቅዱስ ያሬድን ታሪክ ያስመስላል፤ ቢሆንም ሁል ጌዜ የእመቤታችን ስዕል ፊት እየሆኑ ማኅፀናት ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን እመቤታችን ተገልፃ ‹‹አይዞህ አታልቅስ፤ ትምህርት ተከልክሎብህ ሳይሆን የምትጠቀምበት ጊዜው እስኪ ደርስ ነው፤ አሁን ጊዜዉ ደርሷል›› አለችው፤ ‹‹እስከ ፯ ቀን በዚሁ እንዳለህ ጠብቀኝ›› ብለውም ተሠወረች። እርሳቸውም ተስፋውን ተቀብለው በሱባዔ እንዳሉ እንደተለመደው በስዕለ ማርያም ሥር ተደፍተው ሲያለቅሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመልአክት አለቃ ቅዱስ ዑራኤልን አስከትላ ጽዋ እሳት (ጽዋ ልቦና እንዳጠጠው ዕዝራ ሱቱኤልን) የሕይወት ጽዋ አጠጣችው። አባ ጊዮርጊስ የሕይወት ጽዋ ከተጎነጩ በኋላ የሰማይና የምድር ምሥጢር ተገለጸላቸው።
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የደረሱት መጽሐፍት ከሃምሳ በላይ ይሆናሉ፡፡ በስም የሚታወቁት ግን ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት፣ ኖኅተ ብርሃን ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ ታትሟል፣ ውዳሴ መስቀል፣ ቅዳሴ፣ ውዳሴ ሐዋርያት፣ አርጋኖነ ውዳሴ፣ ፍካሬ ሃይማኖት፣ መጽሐፈ ምሥጢር፣ ውዳሴ ስብሐት፣ እንዚራ ስብሐት፣ ሕይወተ ማርያም፣ ተአምኖ ቅዱሳን፣ መጽሐፈ ብርሃን እንዲሁም ጸሎት ዘቤት ናቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የተሞሉ አባት ናቸው፡፡
በዜማ ትምህርት በጣም ጠልቀው ያውቁ፣ የቅዱስ ያሬድን ዜማ በተለይም ድጓውን በዘመናት ከፋፍለው እና በየበዓላቱ አደራጅተው፣ ቅርጽ በማያስያዝ ለቅዱሳኑ ሁሉ በየባህሎታቸው የሚዜመውን አዘጋጅተው ለደቀ መዛሙራቶቻቸው በማስተማር እንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድጓውን በደብር ነጎድጓድ ሐይቅ ለሰባት ፯ ‹በርእስ አድባራት ተድባበ ማርያም› አስተምረዋል፡፡ በዜማው በኩል አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ከያሬድ በኋላ የተነሡ ዳግማዊ ያሬድ ሲባሉ በዘመኑ የነበሩትን መናፍቃንን በመከራከርና አስተምረው በመርታታቸው ‹ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ› የሚል ስምም ተሰጥታቸዋል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ስለ ሰማይ፣ ስለ መብረቅና ስለ ዝናም አፈጣጠርና ባሕርያት በሚገባ አስተምረዋል፡፡ ሆኖም ግን ድርሰቶቻቸውን የውጭ አንብባቢዎች ሲጠቀሙበት የሀገራችን ሰዎች ግን የታላቁን ቅዱስ ታሪክ እንኳን በቅጡ የማያውቅ ነው፡፡ እርሳቸው ግን የቤተ ክርስቲያን መብራት ናቸው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱ፣ በምሥጢሩና የምስጋና ድርሰቶች አሁንም ቤተ ክርስቲያን እየተጠቀመችባቸው ትገኛለች፡፡ ይህ ሕሙም ትውልድ መድኃኒት ያስፈልገዋለና መድኃኒቱን ለማግኘት ሌት ከቀን በመጾም፣ በመጸለይና መትጋት እንዳለበት በአጽንዖት አስተምረዋል፡፡አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በአጼ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥትም ‹‹ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ተጠያቂ ሊቅ›› ተደርገው ተሹመው ነበር፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የትሕት፣ የርኅራኄና የምሥጢር ባለቤት አባት ናቸው፡፡ የርኅራኄ አባት ያልንበት ምክንያት እንዲህ ነው፤ በአንድ ወቅት ሳያመነኩሱ ገና ንጉሥ ዳዊት ልጃቸውን እንዲያገቡና በእርሳቸው ቦታ እንዲተከቱ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ እርሳቸውም የንጉሡን መልክእት በመስማትና ያሞክሮ ልብስ በመልበስ የመጣባቸውን ፈተና አልፈውታል፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሥ ዳዊት ስላልሰሟቸው ብዙ መከራና ሥቃይ አድርሰውባቸዋል፡፡ ግን እኚህ ንጉሥ መስቀሉን ሊያመጡ ሲሄዱ ጎዳና ላይ በቅሎ ረግጣቸው ሞቱ። አባ ጊዮርጊስም የንጉሡን ሞት በሰሙ ጊዜ ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡ ‹‹ምነው ያ ሲያንገላታህ፣ ብዙ መከራ ሲያደርስብህና በጨለማ ቤት ሲወረውርህ ደስ ሊል ይገባል እንጂ እንዴት ታለቅሳለህ?›› ብሎ ሰዎች ሲጠይቋቸው ‹‹እንደዚያም ቢሆን ንጉሡ እመቤታችንን ይወዱ ስለነበረ ነው ያዘንኩት›› ብለው መልሰውላቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ‹‹የእግዚብሔር መንገድ ቅን ነው። ጻድቃን ይሄዱበታል፡፡ ሕግ ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል፤›› ተብሏል፡፡ (ሆሴ.፲፬፥፱)
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተወለዱ በ፷ ዓመታቸው ኢትዮጵያ አበቅቴ አልቦ በሆነበት ጊዜ ጥንተ ዮን በወንጌላዊው ማቴዎች ዘመን ረቡዕ ቀን ይስሐቅ በነገሥ በዐሥራ አንድ ዓመት በ፲፬፻፰ ሐምሌ ፯ ቀን ዐርፈዋል፡፡
የጻድቁ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን፤ አሜን፡፡
መምህር ሰሎሞን ጥጋቡ
ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የሰኞ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ከባረከችው በኋላ ምስጋናውን የጀመረው “ፈቀደ እግዚእ…” ብሎ ነው፡፡
፩. በመቅድመ ወንጌል “ ወ አልቦቱ ካልእ ሕሊና ዘንበለ
ብካይ ላዕለ ኃጢያቱ - በኃጢአቱ ከማዘን፣ ከማልቀስ በቀር
ሌላ ግዳጅ አልነበረውም” እንዲል ጌታ ፭ ሺህ ከ፭፻ ዘመን
በግብርናተ ዲያብሎስ ያዝን ይተክዝ የነበረ አዳምን ነጻ
ያደርገው (ያድነው) ዘንድ ወደደ፡፡ ምድራዊ ንጉሥ የተጣላውን አሽከር “ሰናፊልህን (ልብስህን) አትታጠቅ፤
እንዲህ ካለ ቦታም አትውጣ” ብሎ ወስኖ ያግዘዋል፡፡
በታረቀው ጊዜ ግን ርስቱን፣ ጉልበቱን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን
እንደሚመልስለት ኹሉ ንጉሠ ሰማይ ወምድር
እግዚአብሔርም “ጥንቱንም መሬት ነህና ወደ መሬት
ተመለስ” /ዘፍ.፫፡፲፱/ ብሎ ፈርዶበት የነበረ አዳምን ይቅር
ብሎ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ
ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ወደደ /ሉቃ.፳፫፡፵፫/፡፡
ሊቁ (ቅዱስ ኤፍሬም) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ፫ ቁጥር
፱ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕምም እንዲህ ይላል፡- “ቸር
ወዳጅ የኾነው እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ወዲያው
እንደተሳሳቱ ፍርዱን አላስተላለፈባቸውም፤ ታገሣቸው
እንጂ፡፡ ይኸውም ምኅረት ቸርነቱን ይለምኑት ዘንድ ነው፡፡
እነርሱ ግን አልለመኑትም፡፡ እግዚአብሔርም ምንም
ሳይናገራቸው በገነት ውስጥ በእግር እንደሚመላለስ ሰው
ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ አዳምና ሔዋን ግን
አሁንም አልመለስ አሉ፡፡ በመጨረሻም አምላክ ድምፁን
ማሰማት ጀመር፡፡ ‘አዳምን ወዴት ነህ?’ ይላቸው ጀመር፡፡
አስቀድሞ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ
መጥራቱ መንገድ ጠራጊው ዮሐንስን እንደሚልክላቸው፣
ቀጥሎ ድምፅ አሰምቶ ወዴት ነህ ብሎ መፈለጉም ወልደ
እግዚአብሔር ራሱ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ኾኖ
ሊያድናቸው እንደ ፈቀደ ያጠይቃል” ይላል /St. Ephrem
the Syrian, Commentary on Genesis/፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ኦሪት ዘልደትን በተረጐመበት
በ፲፯ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “በዚህ ንግግሩ የእግዚአብሔር
ከአእምሮ የሚያልፈውን ፍቅሩን እንመለከታለን፡፡ አንድ
አባት ልጁ የማይረባውን ነገር በማድረግ ከክብሩ
ቢዋረድም አባቱ እጅግ እንዲወደውና ወደ ቀደመ ክብሩ
ይመልሰው ዘንድ እንዲደክም፤ እግዚአብሔርም ከሰው
ልጆች ጋር ይህን የመሰለ ፍቅር ሲያሳይ እናስተውላለን፡፡
አንድ ሐኪም ወደ ታማሚው አልጋ ጠጋ ብሎ በሽተኛውን
እንዲጠይቀውና አስፈላጊውን ኹሉ እንደሚያደርግለት፣
ሰው ወዳጁ እግዚአብሔርም ወደ አዳም ጠጋ ብሎ
ሲያነጋግረው እንመለከታለን” ይላል፡፡
ዳግመኛም በሌላ አንቀጽ “አዳም ሆይ ወዴት ነህ”
ማለቱ፣ ለአቅርቦት መኾኑን ሲገልጥ፡- “አዳም ሆይ! ምን
ኾንክብኝ? በመልካም ቦታ አስቀምጬህ ነበር፤ አሁን ግን
ቦታህ ተለወጠብኝ፡፡ ብርሃን ተጐናጽፈህ ነበር፤ አሁን ግን
ጨለማ ውስጥ አይሃለሁ፡፡ ልጄ! ወዴት ነህ? ይህ ኹሉ
እንደምን ደረሰብህ? በአንተ ውስጥ ያኖርኩት መልኬ ማን
አበላሸብኝ? በዚህ ያህል ፍጥነት የጸጋ ልብስህን ገፎ
የጽልመት ልብስ ያከናነበህ ማን ነው? ውዴ! ባለጸጋ
አድርጌ ፈጥሬህ አልነበረምን? ታድያ አሁን ድኽነት ውስጥ
የከተተህ ማን ነው? ያን የግርማ ልብስህን ሰርቆ
ዕራቆትህ ትኾን ዘንድ ያደረገህ ማን ነው? እኮ የጸጋ
ልብስህን እንድታጣ ያደረገህ ማን ነው? ይህን የመሰለ
ቅጽበታዊ መለወጥ ከወዴት መጣብህ? የከበረ ዕንቁህን
እንድትጥል ያደረገህ ምን ቢገጥምህ ነው? አክብሮ
በተወደደ ቦታ ካስቀመጠህና ኹል ጊዜ በስስት ዐይን
ሲያነጋግርህ ከነበረው አምላክህ ተደብቀህ እንድትሸሸግ
ያደረገህ ምንድነው? ማንም የወቀሰህ ሳይኖር፣ እንዲህ
እንዲህ
#ብሒለ_አበው
✍️"ሥር ሳይኖረው መልካም ተክል ሊኖር እንደማይችል ሁሉ ያለ ምሥጢራት ሊኖር የማይችልም ጸሎት የለም፣ በተለይም ያለ ቅዱስ ቁርባን" (📚አቡነ ሺኖዳ)
✍️"ለቤተ ምኩራብ የሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት በቅዱስት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የታወቁና የተረዱ ናቸው፤ ምኩራብ ዘራች፤ ቤተክርስቲያን አጨደች፤ ምኩራብ ፈተለች፤ ቤተክርስቲያን ለበሰች" (📚አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ)
✍️"በልቡ በሌላው ላይ የሚፈርድና አፍንም በርሱ ላይ የከፈተ፣ በወንድሙ ላይ በፈረደበት ኃጢአት እርሱም ይወድቁበታል፤ መለኮታዊ ጥበቃ እርሱንም ስለፈራጅነቱ ይለየዋልና" (📚ቅዱስ ደሮዚዮስ)
✍️"ለሰውነትህ ዕረፍትን ታገኝ ዘንድ ዘወትር ቅዱሳት መጻሐፍ መመልከት ውደድ" (📚ማር ይስሐቅ)
✍️"እንዴት በሚገባ መያዝ እንዳለበት አንድ ሰው ካላወቀ ሐብት እባብ ነው፤ እባብን ዝም ብለው ሳይጠነቀቁ ከጀርባው ጫፍ ከያዙት እጅ ላይ ተጠምጥሞ እንደሚነድፍ ሐብትም በጥበብና በጥንቃቄ ካልያዙት እንዲሁ ነው" (📚ቀለሚንጦስ ዘእስክንድርያ)
✍️"ሰው ልቡን ካልጠበቀ የሰማውን ሁሉ መርሳትና መዘንጋት ይጀምራል፤ ስለሆነም ጠላት በርሱ ውስጥ ቦታ ያገኛል፣ ገልብጦም ይጥለዋል ልክ ዘይት ተሞልቶ እንደሚያበራ መብራት ማለት ነው" (📚አባ አርሲየስ)
✍️"እግዚአብሔርን መፍራትና ትህትና ከሁሉም የሚበልጥ መልካም ሥራ ነው" (📚አባ ዮሐንስ ሐጺር)
✍️"ከዕውቀት ክብር የተለየች ማለት በእውቀት ከሚሠራ ትህትና የተለየች ሰውነት በትዕቢት መከራ ትያዛለች" (📚ማር ይስሐቅ)
✍️"በፈተናዎች ባልተፈተንን ጊዜ ራሳችንን የበለጠ ማዋረድ ይኖርብናል ምክንያቱም እግዚአብሔር ደካማነታችንን አይቶ እየጠበቀንና ፈተናውን እያስቀረልን ነውና፤ ራሳችንን ከፍ ካደረግን ግን ጥበቃውን ከእኛ ያርቅብንና እንጠፋለን" (📚አረጋውያን)
✍️"ምድር ከሁሉም በታች ስለሆነ ካለበት ወደ ታች አይወርድም፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግም እንዲሁ አይጣልም፤ ዝቅተኛ የሆነች ምድር ውኃን ትቀበላለች፣ ራሱን በትሕትና ዝቅ የሚያደርግም እንዲሁ ከሁሉም በላይ ይጠቀማል፣ በክርስቶስ ቀኝም ያለ ነቀፋ ሆኖ ይቆማል" (📚አባ ጴሜን)
#ምንጭ፦ 📚ብሒለ አበው
ከነሐሴ 1 እስከ 15 #ፆመ_ፍልሰታ_ለማርያም
👉አንድ አምላክ በሆነ #በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም ለእናታችን #ማርያም ፆመ ፍልሰታ እንኳን አደረሰን
👉በቤተ ክርስቲያን ከሚጾሙት የዐዋጅ አጽዋማት ውስጥ አንዱ የሆነው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም የእመቤታችንን ትንሣኤ እና ዕርገት ምክንያት በማድረግ ለ15 ቀናት የሚጾም ነው
👉ይህም አምላክን በድንግልና የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በለበሰችው ሥጋ በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች ሐዋርያት ሥጋዋን ለመቅበር ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘው ሲሔዱ ለቅናት የማያርፉት አይሁዶች ሥጋዋን ለመቀማት ሲነሡ ታውፋንያ የተባለው የጎበዝ አለቃ ቀድሞ በመድረስ የአልጋውን ሽንኮር በመያዝ ሊጥላት ሲሞክር #መልአከ_እግዚአብሔር ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡
👉ሥጋዋንም ነጥቆ ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወደ ገነት አሳረገው ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሩት ዘንድ ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ እስከ 14 ቀን ሁለት ሱባኤ ይዘው በ14ኛው ቀን ሥጋዋን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጸሎትና በደስታ በጌቴ ሴማኒ አሳረፏት፡፡
👉ከመቃብር ስፍራውም ተነሥታ ስታርግ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ አያት ለሐዋርያትም እንዲነግራቸው ለማስረጃነት እንዲያሳያቸው ሰበኗን ሰጥታው ዐረገች በዓመቱ ሐዋርያት ተሰብስበው ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እኛስ እንዴት ይቀርብናል በማለት ሱባኤ ገቡ ከዚያም ጌታችን ልመናቸውን ሰምቶ እመቤታችንን አምጥቶ አሳይቷቸዋል፡፡
👉በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ጾም ምክንያት በማድረግ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 14 የሌሊት ሰዓታት ይቆማል፣ የጠዋት ስብሐት ነግህ ይደረሳል፣ የውዳሴ ማርያምና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜም ይተረጎማል ከዚህ በተጨማሪ ቅዳሴ ከሳምንት እስከ ሳምንት አይታጎልም፡፡
👉በጾመ ፍልሰታ ብቻ የሚተረጎመው ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም በዋናነት የጾሙ ስያሜ ጾመ ማርያም በመባሉና እግዚአብሔር ለእመቤታችን የሰጣትን ክብር ለማሳወቅ ይረዳ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዓቱን እንደሰሩት ይነገራል፡፡
👉በተጨማሪም በቅዱስ ኤፍሬም የተደረሰው ውዳሴ ማርያም ነገረ ክርስቶስንም የሚያሳየን የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ነው በዚህም ስለ ክርስቶስ ጽንሰት፣ ልደት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገት ይናገራል ከዚህም አልፎ ምእመናን ምሕረት እንዲያገኙ እመ አምላክ በተሰጣት ቃል ኪዳን ይቅርታን እንድታሰጥና እንድታማልድ “ቅድስት ሆይ ለምኝልን” የሚል ፍጻሜ ስላለው እንደሆነ አባቶች ያስረዳሉ
👉በተያያዘ ቅዳሴ ማርያም አባ ሕርያቆስ የደረሰው ሲሆን እንደ ውዳሴ ማርያም በቤተ ክርስቲያን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የኖረ ነው ቅዳሴ ማርያም ምስጢረ ሥላሴ፣ ነገረ ክርስቶስ፣ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮን አሟልቶ የያዘ ነው፡፡
👉ይህም ሲጀምር የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያና የሁልጊዜ ትምህርቷ በሆነው በምስጢረ ሥላሴ ነው፡፡ በዚህም “ጎሳ ልብየ፣ ጎሳ ልብየ፣ጎሳ ልብየ” ብሎ አንድን ቃል ሦስት ጊዜ በመደጋገም የሥላሴን ማንነት በአካል ሦስት በመለኮት አንድ መሆኑ የተገለጸበት ድርሰት ይገኛል፡፡
👉ስለዚህ በጾመ ፍልሰታ ቅዳሴ ማርያም መተርጎሙ አንዱ ምእመናን የሥላሴን አንድነት እና ሦስትነት እንዲረዱ ስለሚረዳ እንደሆነ ይገለጻል እኛም የእመቤታችን ምልጃና ጸሎት የሐዋርያት በረከት ይደርሰን ዘንድ እንጾማለን
👉አምላካችን መድኃኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለሀገራችን ለቤተክርስቲያናችን ለህዝባችን ሠላሙን ፍቅሩን ይሰጠን ዘንድ ቅድስት ሆይ ለምኝልን "አሜን"
ሐምሌ 29/2015 #ፃድቁ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ
👉አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለፃድቁ አባታችን አቡነ እጨጌ ዮሐንስ ዘጠገሮ አመታዊ የእረፍት በአል መታሠቢያ እንኳን አደረሰን
👉ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡
👉አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ ‹‹በምን አውቀኸኝ ነው?›› ብላ አቅፋ ሳመችውና ‹‹ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 አመት ትኖራለህ" ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡
👉ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዮሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኋላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኩስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖረዋል
👉ከዚኽም በኋላ አባ ዮሐንስ ወደ ተዘጋቸላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኋላ ይገኛል፡፡
👉ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡
👉የፃድቁ አባታችን ታሪክ ከብዙ በጥቂቱ ይህን ይመስላል
👉የአባታችን ፀሎትና ልመና ሀገራችንን ህዝባችንን ከክፉ መከራ ይሠዉርልን የከበረዉ ቃል ኪዳናቸው ሁላችንንም ይጠብቀን የተባረከ #ቀዳሚት_ሰንበት ይሁንልን "አሜን"
✝ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ✝
✝ #ሐምሌ ፳፱ (29) ቀን።
✝ እንኳን #ለታላቁ_አባት በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 ለኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት ለተደመሩ ጻድቅ #ለእጨጌ_እጨ_አቡነ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ_ለዕረፍት በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
✝ #እጨጌ_እጨ_አቡነ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ፦ ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ "በምን አውቀኸኝ ነው?" ብላ አቅፋ ሳመችውና "ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ዓመት ትኖራለህ…" ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡
✝ ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዩሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኋላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኵስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዮሐንስ ወደ ተዘጋጀላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡
✝ ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡
✝ አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚህም በኋላ "ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?" ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም "አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?" አሏት እርሷም "አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?" አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው "በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ" ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ "የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ" ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለተሃማኖት ሔዱ፡፡
✝ አቡነ ዮሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምሕረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡
✝ አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም መቋሚያቸው በመዳበስ በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዮሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኋላ ዕረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋርያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ "ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኵሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…" የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
✝ ቅዱስ አባታችንም በ 500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው "በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም" አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ 134 ዓመት በኋላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡