መጨከን አቃተኝ
ልረሳት ሞከርኩኝ
ከልቤ ላወጣት
ስለ'ሷ ላላስብ ፥ ዳግመኛ ላላያት፤
.
.
ለካስ አትረሳም
ከልብም አቶጣ
ብፈልግ ባስፈልግ ፥ ለ'ሷ እንከን ታጣ፤
.
.
ልጠላትም ሞከርኩ
መጥፎዋን ፈልጌ
ከር'ስቷ ላባራት ፥ ከልቤ ዳር ግርጌ፤
.
.
በምን አሳብቤ
እንደምንስ ልጥላት!?
እንዲው በደፈናው ፥ ያለምንም ምክንያት፤
.
.
የማትጠላ አርጎ
ፈጣሪ ፈጥሯት
በሷ የሚጨክን ፥ አጣውኝ ጉልበት።
#ከመሰለ_ከልካይ
"ጉራማይ"
"የምሰራች"
ዮም:ፍስሀ:ኮነ:በእንተ:ልደቱ:ለክርስቶስ!! ትህትናን፣ፍቅርን የሰውን ዋጋ በበረት በመወለድ:አስተማረን!!
ወልድ:ሲወለድ:የሰው:ልጅ የሚፈልገውን: አምላክነት:በእሱ:አገኘ::
ውድ የግጥም ቃና ቤተሰቦች እንኳን ለብርሀነ ልደቱ በሰለም አደረሰህን 🙏 መልካም በአል
@ilovvll
@ilovvll
@ilovvll 👈 ቤተሰብ ይሁኑ
አብሮነትዎም አይለየን
በሀገራችን፡ፍትህ፡ስደተኛ፡ናት።
ከሰው፡ልብ፡ሸሽታ
በገዥዎች፡ሸንጎ
ጥገኝነት፡የምትጠይቅ
ደጅ፡ጠኝ፡ሆናለች።
ራስ፡ወዳድነት፣አስመሳይነት፡እና
ስስት፡ተበራክተው፡ፍትህን፡አደቀቋት፤
ደበደቧት። መውጫ፡መግቢያ፡ነሷት።
ሸሸች። ከሰው፡ልብ፡ጠፋች።
ከሜዳ፡ሜዳ፡ስትዞር
ከመንግስት፡ስር፡መጠጊያ፡አገኘች።
መንግስት፡ደግሞ
እንደማንኛውም፡ስደተኛ
ንብረቱ፡አደረጋት፡፡
ሲያሻው፡ሰጥቶ
ሲያሻው፡የሚነፍጋት፡ሆነች።
ሰው፡ከልቡ፡ያለውን፡ፍትህ፡አባርሮ
መንግስትን፡መልሰህ፡ስጠኝ፡ቢል
ከየት፡ይሰጠዋል?
ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ
@kene_tobeya
እንደምትወዳት ንገራት
ሕይወት የብድር በሬ፥መቼ ሁሌ ይጠመዳል
ለጊዜው ብቻ የመጣ፥ ጊዜው ሲደርስ ይሄዳል
የተሰጠህ ጸጋ ሁሉ፥ ደሞ ካንተ ይወሰዳል::
ቀለበት፥ አምባር አይደሉም
እጅህ ላይ ሁልጊዜ የሉም
-ቀናት ሳምንታት ወራት
ዛሬውኑ ፥አሁኑኑ፥ እንደምትወዳት ንገራት::
አበቦች ሁሉ ሳይረግፉ
ምኡዝ ሽታዎች ሳይጠፉ
ያጸድ በሮች ሳይቆለፉ
በንቦች ጎዳና ላይ፥ተርቦች ሳይሰለፉ
በንፋስ ክንፍ ሳይመታ
ሕይወት የላምባ መብራት
አሁንኑ ዛሬውኑ ፥እንደምትወዳት ንገራት፤
ርቃ ሳትገሰግስ
ገና ስንቋን ስትደግስ
እንዲሁ እንዳማረባት
ቀልብህ እንደቀረባት
መቃብር በመዳፉ
እንደጠጠር ሳይቀልባት
አፈሩን ሳትዛመድ
ወደማትቀባው አመድ
ወደማትስበው አየር
ሳትቀየር
አንተም አንደበት ሳለህ፥ እሷም ጆሮ ሳያጥራት
ዛሬውኑ! አሁኑኑ! እንደምትወዳት ንገራት ::
በእውቀቱ ስዩም
@kene_tobeya
@kene_tobeya
ተስፋሽን ፈራሁት (በድሉ ዋቅጅራ)
የደጅሽ አበባ፣ እምቡጥ ሲይዝልሽ፤
የታቀፍሽው ህጻን፣ ጠብቶ ሲያገሳልሽ፤
ደስታሽን አይቼ፤
ተስፋሽን ቃኝቼ፤
. . . . . .ነገሽን ፈራሁት፡፡
እምቡጥ የሚያመክን፣
አመዳይ
ትላትል
ተምች በሞላበት፤
እንቡጥ የሚቀጥፍ፣
ሰው በሚኖርበት፤
. . . . . . . . . በእኔና አንቺ አለም፤
ማንቦጥ መታጨት ነው፣
መውለድ መከተብ ነው፣
የዘላለም ሀዘን፣ የዘላለም ህመም፡፡
-------------
(የተስፋ ክትባት )
@kene_tobeya
'ለምን አልፈጠርክም..?'ኤፍሬም ስዩም
ሳይደምን ሳይዘንብ ሳይጨልም ሳይነጋ ፤
ምድርና አርያምን ቀድሞ ሳትዘረጋ ፤
ፊተኛው ኋለኛው አልፋና ኦሜጋ ፤
እንዴት ነበር ኑሮህ ስፍራህስ ምኑጋ ?
ምንት ሳይኖር በፊት ኢምንት እያለ ፤
ያሁኑ ዙፋንህ ኪሩብም ከሌለ ፤
ያኔ ያንተ ሀገር ከየት ነበር ያለ ?
ሀገርህ እንዳልል ያኔ ሀገር የለም ፤
ምንም ሳይኖር በፊት ስትኖር በምንም ፤
በእግዚአብሔርነትህ እግዜር ከሌለብህ ፤
ሁሉንም አዋቂ አንተ ብቻ ከሆንክ ፤
ስንት ዘመን ሆነህ ሆነህ ከተገኘህ ?
ፍጥረትስ ነበረ ከመፍጠርህ በፊት ?
ቀድመው የተሰሩ ከሰው ከመላዕክት ?
ካልነበረም ፍጥረት ፤
የዘመናት አምላክ የዘመናት ንጉስ ጥያቄዬን መልስ ፤
ለምን አልፈጠርክም እስክትፈጥር ድረስ ?
.
@kene_tobeya
@kene_tobeya
ተላለፉ ሲለን
**
ከመረዋው ውግረት
ከቃጭሉ ዋይታ እኩል ብንሰማም
በአንድ ደውል ድምፅ
ግለ ህሊናችን አንድ ላይ ቢደቃም
ተላለፉ ሲለን
ፊትና ኃላ እንጂ እኩል አንነቃም።
ይስማዕከ ወርቁ
ከ "የወንድ ምጥ" የግጥም መድብል
@kene_tobeya
@kene_tobeya
ስትናፍቂኝ ፃፍኩት
ያልጣልነው አልነበር ኮተት ነው እያልን፣
ለካ ህይወት ኗሯል ብዙ 'ሚያስከፍለን፣
አልረሳሽምና
አትርሽኝ እያልኩኝ፣
ብዙ ግጥም ፃፍኩኝ።
ያዬ ሰው ይንገርሽ ቃላቶች ተንጋደው እንዳመሰጠሩ፣
አጃሒብ ነው ደግሞ
ፃፍኩት ያልኩሽ ግጥም
የዕድሜ ካብ ላይ ሲጫን ጣዕሙ መጨመሩ፣
እንዲህ ነው እስካሁን...
ከትላንት በፊት የነበረ ሁሉ
አርጅቷል ወይቦ፣
ካልሆነ ፈንድቋል በለምለም ተከቦ።
ብቻ ላለመተው ስትናፍቂኝ ፃፍኩት ፣
ከሄድሽ በኋላ ምንም ነው ያልገባኝ
ምን? ይሆን ግን ያልኩት..
አማኑኤል ደርበው
@kene_tobeya
@kene_tobeya
💪 በወሬው አይፈታም 💪
መከረው ዘከረው ወቀሰው ገሰፀው
ማሰብ እንዲጀምር እሱም ልክ እንደሰው፤
መከረው ዘከረው ወቀሰው ገሰፀው
ይመለስ እንደሆን እሱን ቆጥሮት ከሰው።
ቀን በገሰገሰ ቀን በሄደ ቁጥር
እንኳንስ ሊመለስ እንኳንስ ሊቀየር
ጭራሹን ባሰበት
ጥጋብ እንደዶኬ
አናቱላይ ወቶ ፣ ተንተከተከበት።
ያሸነፈ መስሎት ዝም ቢለው ጊዜ
የተፈራ መስሎት ቢታገሰው ጊዜ
የሃገሬ ጀግና
ደራሽ ጎርፍ ሆነና
ከምድር ላይ ጠርጎ ጨመረው ተከዜ።
ከተምቤን በረሃ እስከሸዋ ድረስ
ያለምንም ከልካይ ቢጨፍር ቢደንስ
የረታ መሰለው የሚያስቆመው ያጣ
የንቦቹን ቀፎ መንጋውን አስቆጣ
አብይ አመረረ ትግስቱን ጨረሰ
ወደቆላ ወርዶ
የጁንታውን ሬሳ ልክ እንደቄጤማ እየነሰነሰ
ምሽጉን ሰባብሮ
ወደፊት አመራ ጀግና ገሰገሰ
ትንግርት እስኪመስል
ያንን ያህል ዘመን እንዲያ እንዳልታገሰ።
ኩሽና መርመጥመጥ ሊጥ መድፋት ነው እንጂ
በጢሻ መሽሎክሎክ መሯሯጥ ነው እንጂ
ዘሎ ዋሻ መግባት መሰወር ነው እንጂ
ጀግንነት በደሙ
ይዞ እንደሚዞረው እንደኢትዮጲያ ልጂ
የጠላት ቅጥረኛ ተላላኪ ባንዳ
ግብስብስ ወምበዴ ቆሻሻ ወራዳ
መች ፊት ለፊት ገጥሞ እንደወንድ ይገላል
ወንድ ሆኖ ተወልዶ መች ወንድ ሆኖ ያውቃል
ጨለማ ጠብቆ ከኋላ ይዋጋል
የጠባውን ጡት መልሶ ይነክሳል
የእራሱን ጉርጓድ
እራሱ አርቆ ሌት ተቀን ይምሳል
ለሞት በገዛ እጁ ግብር ይደግሳል
የሲኦሉን ካርኒ ትኬቱን ይቆርጣል
ጀግና ፊቱ ሲቆም
በሞርተሩ ሳይሆን
በቅዘን በሽንቱ ምድሪቷን ያጠፋል
ያን ጊዜ በጥይት እንኳንስ በአረር
በጠጠር ቢመቱት ባፍጢሙ ይደፋል፤
ጭፈራ እስክስታ
ዳንኪራ እልልታ
"እምበር ተጋደልቲ እምበር ተጋደላይ"
ማለቱን አቁሞ ፣ ይላል ዋይ!! ይላል ዋይ!!
እንደገና ደግሞ
ከተፋበት ጎበዝ ከናቀው ፊት ቆሞ
ምረት ይጠይቃል
ምረት ይለምናል
ምረት ይማፀናል
ባልፀዳ ጉሮሮው ህዝቡን ይማለዳል
እግሮቹ ስር ወድቆ
"ሤጣን አሳሳተኝ" እያለ ይጮሃል
ሤጣን አስተምሮት ሤጣን ያሳስታል!!
በያዙኝ ልቀቁኝ
እሱ እንዳልባሰ በምላሱ ጡንቻ
እንዲያ እንዳልረገጠ
በውዳሴው ከንቱ በምኞቱ ብቻ
ዓጓርቶ እንዳልነበር
ዲቤ እየደለቀ ሆኖ እንደቃልቻ
በሆዱ ደብቆ
በመሪው ያላካል
የራሱን መምበጭበጭ የራሱን ፍራቻ።
እናም
የማንም ቦቅቧቃ የማንም ቅዘናም
የማንም ደምባራ የማንም ቅዠታም
የጎበዝን ጦር
በምላስ ነው እንጂ በጥበብ አይፈታም
የወንድን ወንድነት
በቅጥፈት ነው እንጂ በጉልበት አይረታም
የጀግናን ተጋድሎ
በጡፈት ነው እንጂ በብልጠት አይገታም።
(መሰለ ከልካይ)
ህዳር 2014ዓ.ም
@kene_tobeya
@kene_tobeya
#ለጤዛ_ተዋድቀን!
እድሜያችን ሰባ ነው ፥ ቢበዛም ሰማንያ
ይህም ኑሮ ሆኖ ፥ ጠዋት ማታ ፍልሚያ
አንዱ ካንዱ ጥዋ ፥ ጥቃት የቀመሰ
በየደጃፉ ላይ ፥ ምሽግ እየማሰ
ጦር እንደ ቄጤማ ፥ እየነሰነሰ
መንደሩን ሸንሽኖ ፥ ባጋም እሾህ ቅጥር
ወገን እያስለየ ፥ ባሰለፈን ቁጥር
ጤናችን ሲሸረፍ
ቀናችን ሲዘረፍ
የት ሸሽተን እንትረፍ
የት ገብተን እንረፍ?
በዶፍ ዝናብ አገር ፥ ለጤዛ ተዋድቀን
ሰላም እንደራበን ፥ ደስታ እንደናፈቀን
ትግላችን ሰልፋችን ፥ ያከትማል አንድቀን!
በዕውቀቱ ስዩም
t.me/kene_tobeya
💎የተመረጡ (በተለይ አሁን ካለንበት ሁኔታ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው) የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች ።
በቅድሚያ የሼህ ሁሴን ጅብሪል አጭር የሕይወት ታሪክን ተጋበዙልኝ…
ሼህ ሁሴን ጅብሪል ከ1811- 1908 እንደኖሩ ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ ቤተ (1996፣ vii) በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል። ስለ ሸህ ሁሴን ጅብሪል የሕይወት ታሪክ በስፋት የጻፈ ቦጋለ ተፈሪ ነው:: አቶ ቦጋለ ተፈሪ ፣ ሼህ ሁሴን ጅብሪል ከአባታቸው ከሼህ ጅብሪል በወሎ ክፍለ ሀገር በወረሄመኖ አውራጃ፣ በባዙራ ምክትል በባሆች ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ እምበለ ሴዳ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በ1811 ገደማ ተወልደው በ1908፣ በ97 ዓመታቸው አንዳረፉ ጽፈዋል::
አባታቸው በዘመኑ በቃሉ አውራጃ ታዋቂ ለነበሩት ለገታው ሼህ ቡሽራ አድረው ለሰላሣ ዓመታት በመውሪድነት አገልግለዋል:: (1985፣ 21) ጌታው ሼህ ሁሴን መፍረ የጀመሩት ገና በሰባት ዓመታቸው እንደሆነና የሚናገሩትም መሬት ጠብ እንደማይል ተጽፏል:: አሐዱ
ወይም ቢስሚላሂ ብለው ፍርድ የጀመሩት በአጼ ዮሐንስና በመምሬ ግርማ በተባሉ ቄስ ነው ይባላል። እየታወቁ ሲመጡ ወደፊት የሚሆነውንና የሚመጣውን ከነመፍትሔው መናገራቸውና መተንበያቸው ነበር:: የሚናገሩትም በግጥም ነበር። ከዚያ ነገሥታቱም፣ መሳፍንቱም፣ ትንሹም ትልቁም እሳቸውን መጀን ማለቱን ያዘ። (1985፣ 24)
ግጥሞቻቸውን ከእረኛ እስከ ቃዲ ያውቀዋል፣ ይለዋል:: ሼህ ሁሴን የነቢዩ መሐመድ ተከታይ ነበሩ:: ቢሆኑም እንደ እስላሞች ጫት አይቅሙም፣ ሶላት አያደርሱም፣ መስገጃ ቁርበት፣ ውኃ መያዛ ጦሌ አያንጠለጥሉም:: እንደ ዓባይ ጠንቋይም መጽሐፍ አይገልጡም፣
ጠጠር አይጥሉም:: ግን ሱረት (ሐቀኑር) ያሸታሉ፣ ብርዝ ይጠጣሉ፣ ፍርድም ሲፈርዱ ማለት የሚታያቸውን ሲናገሩ ብርዝ በፎሌ (በሽክና) ይዘው ነበር ይባላል::
***
137. አውራ በሬ ታርዶ አንበሳ ሲያለቅስ
ሐበሻ የዚያን ቀን ትሆናለች ኩስ
ሽታዋ የሚያስከፋ የምታስነጥስ
የዚያን ዕለት ይወድቃል እስላምና ቄስ
የዚያን ቀን ያስፈራል አገር እንዳይፈርስ::
140. ሷሊህና ቃሲም አብደላህና ዙበኗር
በወልቃይት ብቅ አሉ ትግሬ ሲበረበር
ኩታበር ገራዶ ትሆናለች ጠጠር
ጎጃም ትጠፋለች ሳትውል ሳታድር
ብዙ ሰው ይጠፋል ያውም ከባላገር::
141. አሥመራ ተወግቶ ወልቃይት መርዙን ተፋ
ሽሬና መቀሌ ይሆናል የከፋ
እንቅልፍ እንዳይወስድህ እርብ ሳይጠፋ
ይመስላል ላየው ሰው ቂያማ የተደፋ
እርብ ስንቱን ጣለው ጠብቆ ወረፋ::
142. ጋይንት ንፋስ መውጫ ድራና ፎገራ
እርብ ላይ ሞልቶ ሲዘፍን ሲያጎራ
ነጋዴው ይጮሃል መቀሌና አሥመራ
ምን ይበጀው ይሆን ጅልጋና ፎገራ?
ሸዋ ደፈረሰ እህሊን ሳይዘራ::
143. መግዛቱን ይገዛል የዮሐንስ ዘር
ወዲያው ለጥቂት ቀን ይላል ፈንጨርጨር
ተፈሪን ጥላ አርጎ ሲያሳድድ ሲቀብር
ቢያዝ ደግ ነበር አገሩን ሳይቀብር
በቀር ሸዋ አይረጋም አትጠራጠር::
144. ሐበሻ ተፈሪን ይዘው ከቀበሩ
አሥመራ በሞላ ይታጠራል በሩ
መቼም ላስተዋለው ብዙ ነው ነገሩ
እኔ እገሌ አልልም ብዙ ነው ምሥጢሩ
በጫካ አካባቢ መች ቀረ ነገሩ::
145. ሐበሻ ስትደኸይ ስትቀጥን እንደ ድር
አዲስ መንግሥት ወጥቶ ይታደላል ምድር
ኸልቁ የዚያን ጊዜ ይለዋል ደንገርገር
ገንዘቡን ተወርሶ አታክልቱም ሳይቀር
እንኳን የተከለው የበረኻው ሳይቀር::
150. እንኳን የአንበሳ ልጅ እባብ ሲዞረው
ጀግና የሚወጣበት አገሩ የት ነው
ሥፍራውን ለይቼ እኔ ሳስታውቀው
ሽሬ ልጅ አንበራ ማይጨው ወያኔው
ምኒልክ ይመስክር ሲዋጋ ያየው::
159. እያሱ ተረግሞ ሰክሮ ሲያንቀላፋ
ተፈሪ ይነግሣል ሳይደክም ሳይለፋ
ቀጥሎ ያውጃል እንዲያውቁት በይፋ
ፈረንጅን ድል አርጎ ተይዞ ሳይጠፋ
ዘለዓለም የእሱ ናት እስኪሆን አንጋፋ::
160. ሐበሻ ክፉ ነው ቆርጦ ከተነሣ
ፈረንጅን አረጉት ባንዴየ እንዲነሣ
ጦርነት አስቦ ዳግሚያ እንዳይነሣ
አገር መች ይቻላል ቆርቶ ከተነሣ
ሲያዩት ሞኝ ይመስላል ሲነሣ እንደ አንበሳ::
162. አሥመራና ትግሬ ስትል ሰገደይ
እባብ ከተፍ ይላል ማምጫው ሳይታይ
ሸዋ የዚያን ጊዜ ይላል ዋይ! ዋይ!
ጀርባውን ምች መታው ወደ ትግሬ ሲያይ::
186. አጼ ኢያሱ ነግሦ በሸዋ መሬት
ጥቅልል አርጎ ይዞ የአያቱን ግዛት
በኋላ እንደገና አላህ ሽቶበት
ዘኒ ሆነ ብለው በቀን በሌሊት
አይቶ እማይለቅ ሆኖ የምታምር ሴት
እንኳን ሌላይቱን እህቱን ጣላት
በሏ በሌለበት እሱ አስረገዛት
ከአልጋው ያወርዱታል በሥራው ክፋት::
188. ታ(ተ)ጥቆ ተሾመ ተፈሪ አባ መላ
ሃምሳ ዓመት ይገዛል ሐበሻን በሞላ
የሚገዛበት ነው በብልሃት በመላ
ባይሆን ቀኑ ሲደርስ ሃምሳ ዓመት ሲሞላ
የገዛ አሽከሮቹ ያዝ አርገው በመላ
ከአልጋው ያወርዱታል በችግር ሊቆላ፣
ከዚያ ያበሉታል ቸኮሌ ባቄላ
ችግረን ቅመሰው ጮማህን ሳትበላ::
191. ቸኮሌ እያበሉ እልፍኙ ያስሩታል
ሕዝቡን እንደቀጣ ችግር ያበሉታል
መስከረም አንድ ቀን ደንገት ይይዙታል
አሥራ አምስት ቀን ለዓመት ሲቀረው ይሞታል::
(መስከረም አንድ 1967 ዓ.ም ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ስለወሎ ድርቅ ለአንድ የውጪ ጋዜጠኛ የሰጡት አስተያየት በደርጎች ሁን ተብሎ በቲቪ እንዲተላለፍ በተደረገበት ማግስት ነበር ደርግ አስሮ ዘብጥያ ያወረዳቸው።)
208. ደርጎች አይቀሩም ይመጣሉ፣
ዝመቱ፣ መንገድ ሥሩ፣ መሬትን ክፈሉ እኩል የሚሉ
ሰማዩን በባላ ገድፉት ባይሉ::
215. ጡሩንባውን ነፍቶ አዋጅ ያደርግና
ወንዱንና ሴቱን ክተት ይልና
በመድፍ በመትረየስ ያንደቀድቅና
ይቆላዋል ከዚያ መኻል ያደርግና::
(የጁንታው ፍፃሜ ወሎ ውስጥ ስለመሆኑ በርግጥም ተምብየዋል።)
216. አዋጅ ሊደረግ ሲሉ ክተት
የራሕመት ደመና ያጠለለለት
ማቄን ጨርቄን ሳይል አውድማ ክትት
ባቄላ ፍሬ አለች ዲቃን የሚሏት
ስትቀቀል ውላ ፍላት አይነካት
ከርብ መከራ ጌታ የሚያወጣት፣
አንድ ሺህ ሦስት መቶ ከዘጠና ውስጥ
አራት መቶ ሳይሆን እዚያ ውስጥ ናት
የፍጥረቱ አውድማ እርብ የሚሏት::
218. ነቢ ተናግረዋል ኸይረል በርያት
ክፉ ነፋስ አለች ሐበሻ መሬት
ኸልቁን የምትጨርስ ቀንና ሌሊት
ማእናውን ልንገርህ ንፋስ ያልንበት
ሽብርና ጭንቀት የበዛባት ናት
እጦሩ መካከል አለ አሉ ድንገት::
219. ከርብ ጦርነት ወዲያ ያለቸው ሰዓት
ክብረትና አፊ(ሠ)ያ ናት ደስታ ውበት
ምናልባት ብትተርፍ ከሰዎች ጥቂት::
220. ጥሩም በሽታውም መከራው ብዛት
ይበቃል ነበረ የአንድ ማሳ እሸት
አላህ ላደረሰው በዚያች ዘመናት
አባክህ አድርሰን እረቢል (ግ)አዘት::
(ከጦርነቱ በኋላ ብሩህ ጊዜ ስለመምጣቱ)
አዘጋጅ :- (መሰለ ከልካይ)
ምንጭ :- (ጌቴ ገላዬ (ዶ/ር) )
ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ፥ ጀርመን የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል የአማርኛ ቋንቋ እና የአፍሪቃ ፎክሎር (ሥነቃል) መምህር
ነሐሴ 1996 ዓ.ም (August, 2004)
ዋቢ መፅሃፍት:-
1. ቦጋለ ተፈሪ፣ 1985 ዓ.ም፣ የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች:: አዲስ አበባ፣
2.ፈንታ ሀ. 1985፣ የደብረ ማርቆስ ሙስሊሞች ቂሳ:: ለባችለር ዲግሪ ማሟያ የቀረበ ጥናት፣ የኢትዮጱያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ክፍል።
@kene_tobeya
@kene_tobeya
እንዳልሞት አደራ!
(መሰለ ከልካይ)
የሰፈርሽ ጎረምሶች አንድላይ እንዲያዩን
በራቹ ድረስ ካልሸኘውሽ ብዬ ሳልገግም
የተጨመቀ ሰሊጥ የመሳሰሉ
ጭኞችሽ መሃል ሳልሰጥም
የከንፈሮቼን መሃተም ፣ ከንፈሮችሽ ላይ ሳላትም
እንዳልሞት አደራ!
እንደወደል የአሜሪካን ፖሊስ ውሻ
በመኪና ጎማ ፈንታ አንገትሽ ስር አነፍንፌ
እንደጎሸ ጠላ ባፍጢም የሚደፋ መዓዛሽን
እንደሱዳን ሽቶ ብብቴ ስር ተርከፍክፌ
በመግንጢሳዊ ሃይልሽ እየቃተትሁ
መቀነትሽን ተስገብግቤ ሳልፈታ
ስብ ይሁን ወተት የወጠራቸው ጡቶችሽ
አንድ ጊዜ ላፍታ
አፈ•ሙዛቸውን በደረቴ ላይ ደግነው
ሳይስቡብኝ ቃታ
እንዳልሞት አደራ!
ገልቱ እንደገመደው ጅራፍ
መብረቅ እንደመታው ባሕር ዛፍ
ከመድረቅ ከመቅጠኑ የተነሳ
የቆመ ፖል የመሰለ ሰውነቴ
ጅብ ተንፍሶበት ቀበሮ ፈስቶበት
እንደሄደ ውሻ የነፈዘ ጭንቅላቴ
እንደጥዋት ፀሃይ በሚሞቅ ትንፋሽሽ
እንደኮረንቲ በሚናዘር ሰውነትሽ
"አብቅቶለታል በቃ!" እያለ
ሃገሬው እንደጉድ ሲያወራ
አፈር ሳይሆን ማር ልሼ ዳግም
እንደወያኔ ነፍስ ሳልዘራ
እንዳልሞት አደራ!!!
"ታጋቾቹ"
ሃምሌ 2013 ዓ.ም
የስነፅሁፍ ጥማቶን፣ የአንጋፋ እና የወጣት ደራሲያን ስራዎች የሚቀርቡበት ቻናላችንን በመቀላቀል ይቁረጡ።
@kene_tobeya
@kene_tobeya
አትፅናኝ
(መዘክር ግርማ)
ሞትን አንመልሰዉ፣ እናውቃለን አይሸሽ
ስንት ጥፍራም ኀዘን አይተናል መሰለሽ!
ስንት ጥፍራም ኀዘን፣ እንደማቀይር አምነን
ስንት ጥፍራም ኀዘን፣ እንደማይቀር አምነሽ፤
ዳሩ ታውቂዋለሽ።
፣
አቀጣጡ ክፋት፤
አመጣጡ ም‘ፃት፤
ግን ከሄደው ሁሉ፣ ከተመላለሰዉ
ምን ይባላል ይኼ፣ ባንቺ የደረሰዉ?!
ምን ይባላል ይኼ? አንቺስ ምን ልትባይ?
እኩይ ነዉ እታለም፣ ሽንገላ እንደ ሥራይ።
፣
በእድፋም ጥፍሩ፣ ቧጦሽ ጥፍራም ኀዘን
መፅናናት መመኘት፣ ምንድነዉ መማፀን?
ምንድን ነዉ ዕንባ አባሽ?
ምንድን ነዉ ማገገም?
ዕንባሽን ማድረቂያ፣ አልሰጥሽም ማሐ‘ረም።
እሪ በይ!
ቢል በይ!
ኩርምት በይ–ዋኔ!
ላንቺ መፅናናትን፣ አልመኝም እኔ።
ወይኔ በይ!
ወዮ በይ!
ተይ አልልም ጭራሽ፤
አለመፅናናት ነዉ፣ አንቺን የሚያፅናናሽ!
መዘክር ግርማ
t.me/kene_tobeya
በተስፋ አረማመድ
(መዘክር ግርማ)
የጊዜን ሩጫ ፣ ውሽንፍር ቀናበት
የ'ድሜን ግስጋሴ ፣ ብርሃን ተመኘ
ለ'ድሜና ለጊዜ ፣ ሐሳብ አሸክሞ
ተስፋ ግን ብቻውን ፣ ሲያዘግም ተገኘ ።
በነጠላ ጫማ ፣ በተስፋ አረማመድ
እዩት ወደ ሞቱ ፣ የብልጥ ሰው መንገድ ።
@kene_tobeya
ብቸኛ ሰው የለም፡፡
ይሄ ሁሉ ሰው ስለብቸኝነት
የተዘፈነ የሚሰማው
የተገጠመ የሚያነበው
የተሳለ የሚቃርመው
ወዶ ይመስልሀል?
ከሰው ጋር የጠመመ በምንም ላይቀና
ከብቸኝነት ውሰጥ ምን ደስታ አለና?
ምንም:፡
ብቻ እንዲሁ
ከአብሮነት ስቃይ
ዕንባ ያላባባይ
በአብሮነት ተዛዝሎ
ከመክረም ተቋስሎ
እያለ አሸሸ
ስንቱ ራሱን ዋሸ?
ወዶ ይመስለሀል?
ከአድማስ እስከ አድማስ
ሰው ሀዘኑ ሲማስ
እንዲያው ከራሴ ጋር ልሁነው ልንደደው
ብቸኝነት ዜማን
ለሀገሩ በሙሉ ማነው ያስለመደው?
እንጂ
ዘር የሌለው
የሰው ደም ያልሳበው
ሳቅን ፍንጣቂ
የዕንባውን ጭማቂ
የሚያይለት ያጣ
ብቸኝነት ዕጣ
ብሶት ቆፈን ወርሶት
በየጥቃቅኑ ሆድ አንጀቱን ብሶት
ገና ፈገግ ሲል
ጠፍንጎ እየያዘው ብቸኝነት ከፍንጅ
ብቻውን ተፈጥሮ
ብቻውን የሞት የታለ የሰው ልጅ?
ብቸኛ ሚባለው
ወይ እኛ የተውነው
ቢወርደን ዕንባውን
ወይ እኛን ትተውን
እንደሆን ነውና
ብናበጥር ዘሩን
አውጥተን ብናየው ከሀዘኑ ቀለም
የተተወ እንጂ ብቸኛ ሰው የለም፡፡
@kene_tobeya
ሶፋ ወይስ አልጋ? - አስፈላጊው ነገር ላይ የማተኮር ምስጢር
(“ትኩረት” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)
አንድ ሰው በሚኖርበት ማሕበረሰብ አካባቢ አንድን ጥናት ማድረግ ፈለገ፡፡ ከጥናቱ ሊያገኝ የፈለገው እውነታ ይህንን ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል ትኩረታቸው ከላይ ለሰዎች የሚታየውን ብቻ ቀባ ቀባ ማድረግ የሆነና ለታይታ ብቻ የሚኖሩ ሰዎችን የሕይወት ሁኔታ ማወቅ ፈለገ፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ለታይታ ብቻ ሳይሆን በትክክለኛውና በሕይወት ላይ ለውጥ በሚያመጣው ነገር ላይ የሚያተኩሩ ሰዎችን ሁኔታ መገንዘብ ተመኘ፡፡
ይህንን ሁኔታ በቀላሉ ለማወቅ የሚችልበትን ዘይቤ ሲፈልግ አንድ ነገር ብልጭ አለለት፡፡ በየሰፈሩ እየተዘዋወረ ፈቃድን ባገኘበት ቤት ሁሉ እየገባ አንድን ጥያቄ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ጥያቄው አጭርና ግልጽ ነበር፡- “በቤትዎት ካለው ሶፋ እና አልጋ በዋጋ የትኛው ይበልጣል? እነዚህንስ እቃዎች ሲገዙ ብዙ ትኩረት የሰጡበት የትኛውን ነው? ብዙ ዋጋ ላወጡበት እቃስ ያንን ያህል ዋጋ እንዲያወጡ ያነሳሳዎት ምንድን ነው?” የሚል ነበር፡፡
እነዚህን ሶስት ጥያቄዎች ከጠየቀ በኋላ የሰዎቹን የአኗኗር ሁኔታ በቀስታ ያጤን ነበር፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ ቤቶችን በመጎብኘት ይህንን መጠይቅ ለማቅረብና መረጃ ለመሰብሰብ ወደ አንድ አመት ፈጅቶበታል፡፡ በመጨረሻ ያገኘው መልስ ሲጨመቅ አስገራሚ ስእል አመላከተው፡፡
በዚህ ጥናታዊ መጠይቅ ላይ ከተሳተፉት ሰዎች አብዛኛዎቹ ለገዙት አልጋ ካወጡት ዋጋ ይልቅ በብዙ እጥፍ የከፈሉት ለሶፋቸው ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ግዢውን ሲፈጽሙ ብዙ አማራጭ ለማግኘት ጊዜን የወሰዱትና ብዙ ሰው ያማከሩበት እቃ ሶፎው ነበር፡፡ አልጋ ለመግዛት ካወጡት ገንዘብና ለምርጫ ካሳለፉት ጊዜ ይልቅ በሶፋ ላይ የበለጠ ገንዘብና ጊዜ የማውጣታቸውን ምክንያት ሲጠየቁ የሰጡት መልስ ሲጨመቅ፣ “ሰዎች ሲገቡ የሚያዩት ሶፋውን ስለሆነ ነው፣ አልጋውንማ ማን ያየዋል?” የሚል ነበር፡፡
ግኝቱ ይህ ነው፡- አንድ ሰው በቀን ውስጥ በአማካኝ ሰባት ወይም ስምንት ሰዓታትን በአልጋው ላይ ያሳልፋል፡፡ በቀን በሶፋው ላይ ተቀምጦ የሚያሳልፈው ጊዜ ግን በአማካኝ ከሶስትና ከአራት ሰዓት በላይ አይሆንም፡፡ ስምንት ሰዓታት ሰውነቱን ጥሎበት የሚያሳልፈው ይህ አልጋ የተሰኘው ነገር በአካላዊ ጤንነቱ ላይ ይህ ነው የማይባል ስፍራ አለው፡፡ በተጨማሪም ከማይመች አልጋ የሚመጣ የእንቅልፍ ማጣት ችግር ለቀን ተግባር ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑም እሙን ነው፡፡
አስፈላጊ ከሆኑት በሕልውናችንና በስኬታማነታችን ላይ ዘላቂ ተጽእኖ ከሚያመጡት የሕይወታችን ጉዳዮች ላይ ትኩረታችንን ማንሳት ብዙ አሉታዊ ተጽእኖዎች አሉት፡፡ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ከታይታ ወደማያልፉ ነገሮች እንድንዞርና ብዙ ውድ ነገሮቻችንን እንድናባክን አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ለምሳሌ ጊዜአችንን፣ ገንዘባችንንና ሃሳባችን በተለያዩ ጊዜአዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የመበታተን የሕይወት ዘይቤ ውስጥ እንገባለን፡፡ ትኩረቱን ከጊዜአዊውና ለታይታ ከሆነው ነገር ላይ በማንሳት ወደ አስፈላጊውና ወደ ዘላቂው ነገር ያዞረ ሰው ለጊዜው ሰዎች አይተው የሚያደንቁለት ነገር ባይኖረውም እንኳ ለነገ እንደሚሰራ ያውቀዋል፡፡
ለታይታ መኖር የዘመናችን ችግር ነው፡፡ እኛ በፍጹም ተጠቅመንባቸው የማናውቃቸው እንግዳ ሲመጣ ብቻ የሚወጡት ምቹና ደስ የሚያሰኙ እቃዎቻችን ብዙ ናቸው፡፡ በእነዚህ እቃዎቻችን ላይ የፈሰሰው ገንዘብ የእኛን የኑሮ ጥራት ለማሻሻል መሆን ሲገባው አልፎ አልፎ ብቅ ብሎ ለሚሄድ እንግዳ መደሰቻና “ይህና ያኛው እቃ እኮ አለን” የሚለውን መልእክት በድምጽ-አልባ ንግግር ለማስጮህ ካልሆነ በስተቀር ምን ትርጉም አለው? የማንመገበው እህል ሰው እንዲያየው ደጅ ቢሰጣ ምን ዋጋ አለው? የቤቴን መሰረታዊ ነገር ሳላሟላ በየካፌው ለሰው ብከፍል ትርፉ ምንድን ነው?
በሰው ለመታየት ከመጣጣሬ በፊት በመጀመሪያ የግል ኑሮዬንና የቤተሰቤን ሁኔታ በሚገባ ለማየት መጣጣር ይኖብኛል፡፡ ውጫችንን አይቶ ያደነቀን አይን ለውስጣችን ጤንነት ምንም አይነት መዋጮ አያደርግልንም፡፡ የሶፋችንን ማማር የተመለከተ ሰው ያሳየን መገረም የሚያስገርም እንቅልፍ ትቶልን አይሄድም፡፡ የውጭ ገጽታና ውበት እጅግ መልካምና የራሱ የሆነ ጥቅም ያለው የመሆኑ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ በመጀመሪያ ሊቀድም የሚገባው የአስፈላጊውና የመሰረታዊው የኑሮአችን ሁኔታ መስተካከሉ ነው፡፡
@kene_tobeya
ቃል…
(ሰለሞን ሳህለ)
--------------
ከጎጆው አጠገብ በረንዳው ላይ ቆሞ
ስለሷ እያሰበ ደጋግሞ ደጋግሞ
የጻፈውን ግጥም እያነበበችው
የናፈቀው ፊቷን በእንባዋ አጠበችው
‘’ቃልሽ ቀን ነበረው…
ቃልሽ ቅን ነበረው…
ቃልሽ ቀን ገደለው…’’
የሚለውን መግብያ ዘጠኝ ጊዜ አንብባ
ቃሏንና ቀኗን አንድ ላይ አስባ
መአልትና ሌቱን አንድ ላይ ሰብስባ
የገደለችውን ቀን ልክ እንዳወቀችው
የናፈቀው ፊቷን በእንባዋ አጠበችው
‘’ሕይወት ውጣ ውረድ የትሙ ብዙ ነው
ቀን የገደልሽውም አውቀሽ ሳታውቂ ነው
በፀሀይቱና በጨረቃ መሀል
በሰዓታት እጣ በቀን ማታ ክፍል
ከአንደኛው ትንፋሼ ቀጣዩ ሲቀጥል
ስጠብቅሽ ነበር ከእስትንፋሴ እኩል
እዛው ነሽ አውቃለሁ እዚህ ነሽ መጥተሻል
ልቤ ገራገር ነው እስከዚህ ያምንሻል!’’
የሚለውን መዝጊያ ዘጠኝ ጊዜ አንብባ
ፎቶ ደብዳቤውን አንድ ላይ ሰብስባ
ፍቅር የሰጣትን በፍቅር አስባ
ልበ ገራገሩን…
ልቡን እንዳደማች ልክ እንዳወቀችው
የናፈቀው ፊቷን በእንባዋ አጠበችው !!!
@kene_tobeya
@kene_tobeya
#ስለ_መፅሀፍ_እንወያይ
በቅርብ ቀን ስለ መፅሀፍ የሚል አንድ መርሐ ግብር ለማዘጋጄት አስበናል።ዝግጅቱ በየሳምንቱ የሚቀጥል ሲሆን በተመረጡ መፅሀፎች ላይ በየሳምንቱ live በድምፅ አሊያም በምስል እንወያያለን።
በመጀመሪያ በየትኛው? መፅሀፍ እንወያይ።
ለጥቆማ @aman_awi ይጠቀሙ
@kene_tobeya
የገፅሽ ብርሃን ቢጠይም ፀዳሉ
ድምፅሽ ቢቀጥንብኝ ቢሰልብኝ ቃሉ
ወዘናሽ ቢማስን ዛሬ ያለውሉ
በእጆችሽ ጨበጠኝ ሐዘንሽ ስዕሉ...
©ጋሽ_ደበበ ሰይፉ
@kene_tobeya
ሲያንዣብብ የሃዘን ጥላ፣
ሲሳል ቃል በዓለሙ ገላ፣
በእርምጃ ወደ እኔነት ካብ ባቀፍኳት ነፍስ ጥልቅ ስር፣
አንኳኳኹ ከክፍቱም ኋላ ነበር ግን እንደምን? ነበር።
አማኑኤል ደርበው
@kene_tobeya
ቀረሽ እንደዋዛ
(ገብረክርስቶስ፡ ደስታ)
እንደ ድመቶቹ…
የትም እንደሚያድሩት
እንደ ስልክ እንጨቶች፣
እንደ ዛፍ ሀረጎች፣
እንደ ቤት ክዳኖች፣
ብርድ አቆራመደኝ ስጠብቅ ስጠብቅ
˝ትመጫለሽ ብዬ…
ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ፣
የልጅነት ዐይኔ ሟሟ እንደ በረዶ
ትመጫለሽ ብዬ ደቂቃ ስቆጥር፣
ትመጫለሽ ብዬ ባዝን ባንጎራጉር፣
ትወጫለሽ ብዬ በበራፍሽ ብዞር፣
ብርድ አቆራመደኝ፣
የመንገድ መብራቶች አይተው አፌዙብኝ፣
ውርጩ ቀለደብኝ፣
ጨለማው ሳቀብኝ።
አለመምጣትሽን አውቀዋል ያውቃሉ፣
መስኮቶች ጨልመው ፣
ቤቶች ተቆልፈው …
ከተማው ሲተኛ አይተዋል ያያሉ፣
አለመምጣትሽን አውቀዋል ያውቃሉ፡፡
@kene_tobeya
@kene_tobeya
በደል
ዝናብ ቢኖር ፥ በጃችሁ
ምን ያደርጋል? ፥ አንዲት ጠብታ ሞታችሁ!
አዝመራችሁን ፥ ወፍ አይቀምሰው
የለማኝ ፥ አቁፋዳ አያውቀው፡፡
እንደሌላው ፥ አንድ አፍ ሲፈጥርላችሁ
አይደል ፥ የበደላችሁ ?
ያዘመራችሁትን እንዳትበሉ
የጉሮሮአችሁ ጥበቱ።
ያላችሁን እንዳድሉ
የእጃችሁ እጥረቱ።
ደበበ ሠይፉ
t.me/kene_tobeya
አትፅናኝ
(መዘክር ግርማ)
ሞትን አንመልሰዉ፣ እናውቃለን አይሸሽ
ስንት ጥፍራም ኀዘን አይተናል መሰለሽ!
ስንት ጥፍራም ኀዘን፣ እንደማቀይር አምነን
ስንት ጥፍራም ኀዘን፣ እንደማይቀር አምነሽ፤
ዳሩ ታውቂዋለሽ።
፣
አቀጣጡ ክፋት፤
አመጣጡ ም‘ፃት፤
ግን ከሄደው ሁሉ፣ ከተመላለሰዉ
ምን ይባላል ይኼ፣ ባንቺ የደረሰዉ?!
ምን ይባላል ይኼ? አንቺስ ምን ልትባይ?
እኩይ ነዉ እታለም፣ ሽንገላ እንደ ሥራይ።
፣
በእድፋም ጥፍሩ፣ ቧጦሽ ጥፍራም ኀዘን
መፅናናት መመኘት፣ ምንድነዉ መማፀን?
ምንድን ነዉ ዕንባ አባሽ?
ምንድን ነዉ ማገገም?
ዕንባሽን ማድረቂያ፣ አልሰጥሽም ማሐ‘ረም።
እሪ በይ!
ቢል በይ!
ኩርምት በይ–ዋኔ!
ላንቺ መፅናናትን፣ አልመኝም እኔ።
ወይኔ በይ!
ወዮ በይ!
ተይ አልልም ጭራሽ፤
አለመፅናናት ነዉ፣ አንቺን የሚያፅናናሽ!
@kene_tobeya
@kene_tobeya