Support channel for mental health awareness in Ethiopia. We post facts about psychology and psychological phenomenon. ''There is no health without Mental Health.'' Contact @FikrConsultSupportbot
የማህበራዊ ፍርሃት (Social phobia) ስቃይ - ሌሎችን መፍራት
አንድ የ39 ዓመት ሰው ወደ ቢሮዬ መጣ በማህበራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ጭንቀት እና ፍርሀት ይህም እንዴት ከቤት ወቶ መግባትን እንኳን ከባድ እንዳረገበት፣ በሥራ ቦታ ጥሩ አፈጻጸም ማሳየት እንዳይችል እንዴት እንደሚታገለው፣ ሀሳቡን በነፃነት መግለፅ፣ ያላመነበትን እምቢ ማለት ወይም የፍቅር ግንኙነት መመሥረትን አስቸጋሪ፣ ከባድ እንዳረገበት በጭንቀት ተሞልቶ ይገልፅ ነበር።
ከዚህም በተያያዘ ለራሱ ዝቅተኛ ግምት መስጠት፣ የድባቴ ስሜት፣ ተስፋ መቁረጥ እና የዋጋ ቢስነት ስሜት እና መገለል፣ ከቤተሰብ ስብሰባዎች መራቅንም አስከትሎበታል። ጭንቀቱ በጣም ከባድ ስለነበር የስልክ ጥሪዎችን እንኳን አይቀበልም ነበር።
በተጨማሪም የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት፣ ለማግባት ወይም ልጅ ለመውለድ እንደማይፈልግ ያለውን እምነት ገልጿል። በእሱ ቃላት "እኔ አባቴን እሆናለሁ" በማለት አባቱ ከሌሎች ልጆች ወይም ጎረቤቶች ጋር እንዳይገናኝ ይከለክሉት እና ያስፈራሩት እንደነበር ገልጿል። ስለዚህም እሱ ልጅ ቢወልድ እንደሱ በሶሻል ፎቢያ ከሚሰቃዩ ባልወልድስ አለ።
ይህ ታሪክ የማህበራዊ ጭንቀት ጥልቅ ስቃይ እና በአንድ ሰው ህይወት ላይ ያለውን ተጽእኖ ያሳያል..ትርጉም ያለው ግንኙነት እንዳይፈጥር እና ግላዊ እርካታን እንዳያገኝ ይከላከላል።
መልካም ዜናው የማህበራዊ ጭንቀት ዲስኦርደር ሊታከም የሚችል ነው። ውጤታማ ህክምናዎችም አሉት ለምሳሌ የንግግር ህክምና like CBT እና የመዳኒት ህክምና like SSRIs ያሉ መድሃኒቶችን ያካትታሉ።
እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው በማህበራዊ ሁኔታዎች ከከፍተኛ ፍርሃት ጋር እየታገሉ ከሆነ፣ እባክዎን ከአእምሮ ሀኪም ወይም ከስነ ልቦና ባለሞያ እርዳታ ይጠይቁ። ብቻዎን መሰቃየት የለብዎትም - እርዳታ አለ።
ዶ/ር ይቅናሸዋ ሰለሞን (የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
ከመጠን ያለፈ የወላጆች ጣልቃ ገብነት (Helicopter Parenting)
ሁላችንም ልጆቻችን ከጎጂ ነገሮች ሁሉ ተጠብቀዉ አድገዉ ስኬታማ የሆነ ህይወት እንዲኖራቸዉ አብዝተን እንሻለን። ከዚህ ፍላጎታችን የተነሳ የልጆቻችን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ከመጠን ያለፈ ጣልቃ ገብነት ይኖረናል፤ ይህን ፈር የለቀቀ ጣልቃ ገብነት በእንግሊዝኛ "Helicopter Parenting" እንለዋለን፤ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ በእጅጉ ያመዝናል።
ከመጠን ያለፈ ጣልቃ ገብነት የምንለዉ መቼ ነዉ?
- እያንዳንዱን የልጅ እንቅስቃሴ ወይም ዉሳኔዎች በየደቂቃዉ መከታተል ወይም አላፈናፍን ማለት።
- በየእለቱ የሚገጥማቸዉን ፈተናዎች ማሻገር። ለምሳሌ የቤት ስራን ወላጅ ሰርቶ ሲልክ።
- በጣም ቀላልና በልጆች ላይ ምንም ጉዳት የማያመጡ ምርጫዎችን በልጅ ስም ወላጅ ሲመርጥ። ልብስ፣ ምግብ፣ መጫወቻ ወዘተ...
- ዉድቀትና ችግር በፍፁም እንዳያጋጥማቸዉ ሁሌ ጣልቃ እየገባን ስንከላከል።
ታድያ እነዚን ብናረግ ልጆቻችን ላይ የምን እክል ይገጥማቸዋል ያላችሁ እንደሆነ..
- በራስ አለመተማመንና ራስን ችሎ አለመቆም
- ችግሮችን የመፍታት አቅም አለመዳበር
- ዉድቀትን አለመቀበል ወይም የመዉጣት አቅም ማጣት
- ሀላፊነትን ለመዉሰድ ወይም ለመወጣት መቸገር
ስለዚህ ወላጆች ምን ማረግ አለባቸዉ?
- ከፊት ቀድሞ ችግሮችን ማሻገር ሳይሆን መንገድ መምራት
- ከእድሜያቸዉ ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዉሳኔዎችን እንዲወስኑ እድል መስጠት
- በዉሳኔዎቻቸዉ እና በድርጊታቸዉ የሚገጥሟቸዉን መልስ ምታዊ ጫናዎች በተወሰነ መልኩ እንዲያዩ መተዉ።
- ለሚገጥሟቸዉ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ መንገዱን በማሳየት የችግር ፈቺነት ስነልቦናዊ ብቃት እንዲላበሱ ማረግ።
- ከመጠን ያለፈ በእጅጉ አስጨናቂ የሆነ መከታተልን ማስወገድ።
አስታዉሱ!
የወላጅ ሀላፊነት ከልጆቻቸው የህይወት መንገድ ላይ ሁል ግዜ ከፊት እየቀደሙ መሰናክሎችን ማፅዳት ሳይሆን ህይወታቸዉን በተሳካ መልኩ የሚሾፍሩበትን በራስ መተማመን፣ ፅናት እና ራስን ችሎ የመቆም ብቃት ማላበስ ነዉ!
ዶ/ር ሚካኤል ከፍያለዉ
(Sitota Mental Health Care & Rehabilitation Center)
@melkam_enaseb
የመርሃ ግብር ጥቆማ!
ወርሃዊው የሜንታል ሄልዝ አዲስ መርሃ ግብር ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም አትላስ አካባቢ በሚገኘው በአዶር አዲስ ሆቴል ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
አብዛኛው ወላጅ ልጄን እንዴት ብቀጣው ነው አይምሮውን ሳልጎዳ (without causing trauma) ስነስርዓት የማስተምረው የሚል ጥያቄ አለው። ለዚህም የዚህ ወር ርዕስ፡- “ልጆችን መቅጣት እና የአእምሮ ቁስል!” የሚል ሲሆን የዚህ ወር እንግዳችን አቶ አለማየሁ ጥበበ ናቸው፡፡
ለመታደም ይህን መስፈንጠሪያ ይጫኑና ይመዝገቡ፡፡ ⬇️
https://forms.gle/shuEyEKs15r92ENSA
@melkam_enaseb
የልጆች የቋንቋ እና ተግባቦት እድገት ውስንነት!
የልጆች እድገት የምንለካው Gross motor (አካላዊ ጥንካሬያቸውን)፣ Fine motor (ክዋኔያቸውን)፣ Language and communication (የቋንቋ እና የተግባቦት ችሎታቸውን) እንዲሁም Social skills (ማህበራዊ ተግባቦታቸውን) ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
የልጆች የቋንቋ እድገት ፍጥነት የተለያየ ቢሆንም፤ በ ሁለት አመታቸው ቃላትን መመስረት እንዲሁም ከ2 አመት ከግማሽ እስከ 3 ዓመታቸው ድረስ ደግሞ ሃረግን መመስረት ካልቻሉ ወደ ህክምና ተቋም ወስዶ ማሳየቱ ይመከራል።
የቋንቋ እና የተግባቦት እድገት ውስንነት የሚባሉት ህመሞች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ:-
- Language disorder (ቋንቋን ለመረዳት እና ቋንቋን ተጠቅሞ ሃሳብን ለመግለጥ መቸገር)
- Speech sound disorder (የቃላት ድምጸት መዛነፍ/ቃላቶችን በትክክል ለማውጣት መቸገር)
- Childhood onset Speech Fluency disorder/Stuttering (መንተባተብ)
- Social (Pragmatic) communication disorder (የንግግር ዘልማድ ችግር)
እነዚህ ችግሮች ከሌሎች የአዕምሮ እድገት ውስንነቶች (እንደ ኦቲስም፣ ADHD (ትኩረት የማጣት እና የመቅበጥበጥ ችግር)፣ Intellectual developmental disorder..) ጋር አብሮ የመከሰት እና እንደ ምልክት መታየታቸው የተለመደ ነው።
እነዚህ ችግሮች የታየባቸው ልጆች ችግራቸው በመስማት እክል የመጣ እንዳልሆነ መረጋገጥ አለበት።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
የስብዕና ችግሮች ego-syntonic እና Alloplastic ናቸው!
ይህ ምን ማለት መሰላችሁ...የስብዕና ችግሩ ችግር ሆኖ የሚታያቸው ለሌሎቹ እንጂ ለነሱ አይደለም።
ይልቁኑ አንድ የስብዕና ችግር ያለበት ሰው ልቦናው (ኢጎው) ባህርይውን/አስተሳቡን ትክክል እና እንከን አልባ እንደሆነ ይቀበለዋል። በዚህም ምክንያት ለሌሎች እንደችግር የሚታየው ባህርይ በነሱ ዘንድ ምሉዕ እና ትክክል እንደሆነ ይቆጠራል። ይህን ነው ego-Syntoic የምንለው።
ያለባቸውን ችግር እንደችግር ባለመረዳታቸው ራሳቸው ላይ ከመስራት እና ከመቀየር ይልቅ፤ ሌሎችን ለመቀየር እና ወደ እነሱ ባህርይ/አስተሳሰብ ለማምጣት፣ እነሱ ሁሌም ልክ እንደሆኑ: ይልቁኑ የተሳሳቱት በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች እንደሆኑ ለማስረዳት ይሞክራሉ። ይህን ነው Alloplastic የምንለው።
በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ሳብያ የስብዕና ችግር ያለባቸው ሰዎች መፍትሄን ፈልገው ወደህክምና መሄዳቸው የተለመደ አይደለም።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
የእርስዎ የወላጅነት ዘዴና ዘይቤ (Parenting Style) ልዩ-ፍላጎት ባለው ልጅዎ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው አስተውለዋል?
ወላጆች/አሳዳጊዎች ለልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና አላቸው። የወላጆችና የልጆች ግንኙነት (Parent-Child Relationship) በተለይም በልጆች የቀዳማይ የልጅነት ወቅት (Early Childhood Period) ጤናማና የተጠናከረ ካልኾነ መዘዙ አስቸጋሪና ከባድ ይኾናል። ብዙ-ጊዜ ልዩ-ፍላጎት ያለው ልጅ መኾኑ ሲታወቅ ሊደርሱ የሚችሉ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ማለትም፦ ለረዥም ጊዜያት/ዓመታት ችግሩን ሳይቀበሉ መቅረት፣ የቤተሰብ መበታተን፣ የተረጋጋና የተጠና ጥረት አለማድረግ ወ.ዘ.ተ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ተገቢ ድጋፍ/ቴራፒ (Intervention) የማግኘት ዕድል በእጅጉ ይቀንሳል።
በዕድገተ-ሰብዕ የሥነ-ልቡና ጥናት (Developmental Psychology) ዋና ዋና የልጆች የአስተዳደግ ዘይቤዎች፦
1. ወላጅ-መር የአስተዳደግ ዘይቤ
እነዚህ ወላጆች ልዩ-ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ፍላጎት፣ ዝንባሌ እና ጥያቄ የማያዳምጡ ብሎም ጥንካሬና ድክመቶቻቸውን ሳይለዩ እንደነሱ ፍላጎት ብቻ የሚያሳድጉ ናቸው። በዚህም ልጆቹ የሰው ጥገኛ፣ ከሰው የሚጠብቁ ይኾናሉ።
2. ነፃነት የበዛበት የአስተዳደግ ዘይቤ
እነዚህ ወላጆች ልጆች በተሣሣተ ሩቲን ውስጥ ሲገቡ የማያርሙ፣ አላስፈላጊ ባህርይ ሲያሳዩ ችላ የሚሉ፣ አብዝተው ነፃነት የሚሠጡ ናቸው።
3. አሣታፊያዊ የአስተዳደግ ዘይቤ
እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸውን ጥያቄ የሚያስተናግዱ፣ የሚያሣትፉ፣ ሚዛናዊ የሆኑና ሕይወታቸውን በፍላጎታቸው ላይ ተመርኩዘው እንዲኖሩ የሚያስችሉ ናቸው።
4. ቁብ-የለሽ የአስተዳደግ ዘይቤ
ልጆቹ ቴራፒ እንዳያገኙ በቤት ውስጥ የሚተዉ፣ እክሎቻቸው ለመቅረፍ ምንም የማይጥሩ፣ በልጃቸው ላይ ምንም ፍላጎትና ፍቅር የሌላቸው ናቸው።
ሌሎች፦ Helicopter Parenting, Attachment Parenting, Gentle Parenting, Tiger Parenting, SnowPlow Parenting, Free-Range Parenting, Neglectful Parenting, Blending Parenting, Single parent, Nuclear Family, Extended Family, Stepfamily ... ተጠቃሽ ናቸው።
ታድያ ለልጅዎ ምን አይነት ዘይቤ/ዘዴ አለዎት?
አሉታዊ የአስተዳደግ ዘይቤ ልዩ-ፍላጎት ባላቸው ልጆች ላይ የሚከተሉትን ተፅዕኖዎች ሊያሳድር ይችላል፦
▹ በፍጥነት ቅድመ-መፍትሔ (Early Intervention) እንዳይሰጥ፣
▹ ችግሩ/እክሉ እንዲባባስ፣
▹ ተጓዳኝ እክሎች እንዲከሱቱ፣
▹ ድርብርብ/ውስብስብ ዕድገት እንዲኖር፣
▹ ለረዥም ጊዜ የማይፈታ መዘዝ፣
▹ ቴራፒው/ትምህርቱ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል።
በመኾኑም ሁሉም ወላጅ ለተሳካ እና ጤናማ የወላጅነትና የአስተዳደግ ዘዴ የወላጅ ውጤታማ ማድረጊያ ሥልጠና (Parent Effectiveness Training-PET) ቢሠለጥኑ፣ ባለሞያ ቢያማክሩ እና አጠቃላይ የግልና የቤተሰብ ደኅንነታቸውን በመጠበቅ ለልጆቻቸው ዕድገትና ድጋፍ (Intervention) ሊሠሩ ይገባል።
ዋኖስ መስፍን (@WanosMesfin)
የልዩ-ፍላጎት ትምህርት ባለሞያ
@melkam_enaseb
OCPD (Obsessive Compulsive Personality Disorder)
ብዙ ጊዜ OCPD እና OCD ሲምታቱ ይስተዋላል፤ ግን የተለያዩ የአዕምሮ ህመም አይነቶች ናቸው።
OCPD ከ Cluster C የባህርይ መዛነፎች አንዱ ነው፤ በዚህ ስር Avoidant, dependant እና OCPD ይገኛሉ።
የOCPD የባህርይ መዛነፍ ያለባቸው ሰዎች የሚከተሉትን ባህርይዎች ያሳያሉ:-
- ወግ አጥባቂዎች ናቸው። ነገሮችን አድበስብሶ ማለፍ እረፍት ይነሳቸዋል፤ ነገሮችን ከልክ ባለፈ አጽንዖት እና የማያወላዳ ቅደም ተከተል ካልሰሩ አይሆንላቸውም።
- ነገሮች ፍጹም/perfect እንዲሆኑ ይሻሉ፤
- ከመጠን በላይ ሰራተኞች ናቸው። ለነሱ የእረፍት ሰዓት ዘበት ነው። ከስራ ውጭ ህይወት ያለም አይመስላቸው።
- ጥብቅ የህግ እና ስርአት አቋምን ማራመድ መለያቸው ነው።
- ስራዎቻቸውን ግዴታ ካልሆነባቸው በስተቀር በሌሎች አያሰሩም፤ የሌሎች ስራ የማይጥማቸው አይነት ናቸው።
- ቋጣሪዎች ናቸው፥ እጃቸው አይፈታም ይባላሉ..ለክፋ ጊዜ በሚል ሁሌም ገንዘብ እንደቆጠቡ ይኖራሉ።
- የቀረቧቸው ሰዎች 'ግትር እና አዝግ' ናቸው ይሏቸዋል። አንዴ ካሉ አሉ ነው።
ታዲያ ይህ የስብዕና መዛነፍ ያለባቸው ሰዎች እንደሌሎች የስብዕና መዛነፎች ሁሉ ችግራቸው ለራሳቸው ስለማይታወቃቸው (ችግራቸው ego-synotonic ስለሆነ)፥ ህክምና እንዲደረግላቸው የመሄዳቸው እድል አነስተኛ ነው።
ይህም ከምልክቶች መለያየት በተጨማሪ OCD ካለባቸው ሰዎች የሚለያቸው አንዱ ባህርይ ነው (OCD ያለባቸው ሰዎች OCPD ካለባቸው በተሻለ ችግሮቻቸውን ለይቶ የማወቅ እና ህክምና ለማድረግ የመፈለግ አዝማምያ ይታይባቸዋል)።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
ዲፕረሽን ወንዶች ላይ!
የዲፕረሽን ምልክቶች በሴቶችም በወንዶችም ላይ ተመሳሳይ ይሁኑ እንጂ መገለጫዎቹ ይለያያሉ፡፡ የልዩነቱ መንስኤ አስተዳደግ ላይ "ወንድ አይደለህ ቆፍጠን በል!" የመሳሰሉት አባባሎች ስነ ልቦና ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ወይም ተፈጥሯዊ ልዩነት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክኒያት ዲፕረሽን ወንዶች ላይ ሲከሰት በቀላሉ ለመለየት ከማስቸገሩም በላይ የሀፍረት ስሜት ተከትሎት ከመጣ ጥሩ ያልሆኑ ውጤቶች ያስከትላል፡፡
በዲፕረሽን ላይ ሀፍረት ተጨምሮ ሲመጣ ከሰዎች መገለል፣ ስሜትን አውጥቶ ለመናገር አለመቻል (ለቅርብ ሰዎች እንኳ) እንዲሁም የህክምና እርዳታ አለማግኘትን ያስከትላል፡፡ እንዲሁም በዲፕረሽን ምክኒያት የሚመጣውን መከፋት ለመሸፋፈን ወይም ለመቋቋም አልኮልና እና ሌሎች ሱስ አምጪ ነገሮችን አብዝቶ መጠቀም፣ ቁማር አብዝቶ መጫወት፣ ህይወትን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ ማሽከርከር፣ ብስጩ መሆንና በቀላል ነገሮች መናደድ ያስከትላል፡፡ በተለይ ብስጩ መሆን ለቤተሰብ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
የሚወዱትን ሰው ያጡ አንዳንድ ወንዶች 'ጠንከር እንዲሉ' እና ሀዘናቸውን እንዳይገልፁ የሚደረገው ክልከላ እርማቸውን እንዳያወጡና የተወሳሰበ ሀዘን (Complicated grief) ውስጥ እንዲገቡ ሲያደርጋቸው ያጋጥማል፡፡
አብዛኛው ዲፕረሽን ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚታከም በመሆኑ ጥሩ ስሜት ካልተሰማ ወይም የፀባይ ለውጦች ካሉ ከአእምሮ ሀኪም ወይም ከስነ ልቦና ባለሞያ ጋር በመነጋገር መፍትሄ ማግኘት ይቻላል፡፡ የአእምሮ ህመም ፆታ፣ ብሄር፣ የትምህርት ደረጃ ሳይለይ ሁላችንም ላይ ሊከሰት የሚችል፤ ውጤታማ ህክምና ያለው ህመም ነው፡፡
ዶ/ር ዮናስ ላቀው (የአእምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት)
@melkam_enaseb
ጊዜ ሕይወት ሕይወትም ጊዜ እንደሆነ ስንቶቻችን አስተውለናል?
ታድያ ይህን ህይወታችንን በምን አይነት ሁኔታ እየተጠቀምንበት ነው?
በግዜአችን ውጤት እያገኘንበት፤ የምንፈልገውን ነገር እያከናወንበት ነው ወይስ በፍርሃት፣ አሉታዊ ስሜትና ሃሳቦች ታስረን ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ገብቶን ተጨንቀናል?
ለችግሮቻችን መፍትሔ ፍለጋ ላይ ነን?
በልባም ሕይወት ስልጠና ሰዎች እለት ከእለት የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች እንዴት ማሽነፍ እንደሚችሉና በላቀ ትኩረት፤ በልበሙሉነትና ተነሳሽነት ውድ ህይወታቸውን በጥራትና በብቃት በመጠቀም የሚፈልጓቸውን ውጤቶች እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ በጥልቀት እናስተምራለን።
የካቲት 3፣ 2017 የሚጀምረውን የ 60 ሰዓት የልባም ሕይወት ስልጠና ይቀላቀሉን።
ለበለጠ መረጃ ይሄንን ሊንክ በመጫን ልባም ሕይወትን ቴሌግራም ላይ Hi ይበሉን @libam_hiwot0974
ወይም በቀላሉ በዚህ ሊንክ ይመዝገቡ: ⤵️
https://forms.gle/wDEkM5wbeiCSn5Pb7
@melkam_enaseb
አራቱ የህይወት ማዕዘኖች!
ህይወት ምንድን ናት? ዝም ተብላ የምትኖር ወይንስ በዓላማና እና ግብ የተቃኘች? በትኩረት እና በምልዓት የምትኖር ወይንስ ዕለት በቀደደው ቦይ የምትፈስ?
በስነልቦናው አለም ህይወት በአራት ማዕዘናት/ አዕማዳት የተዋቀረች እንደሆነ እና እነዚህ ማዕዘናት ሚዛናቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ይነገራል። ሚዛኑ ወደ አንዱ ካደላ ቅርጽና ይዘቷ ጥሩ አይመጣም።
እነዚህ አራቱ ማዕዘናት የሚከተሉት ናቸው:-
1. መንፈሳዊ ህይወት (Spirituality):- ይህ አምድ በሃይማኖትም ይሁን ያለ ሃይማኖት የሚኖሩ መንፈሳዊ ክዋኔዎችን ይመለከታል። አምልኮ፣ ምስጋና፣ ዮጋ፣ ሜዲቴሽን፣ ውስጥን ማድመጥ.. የመሳሰሉትን።
2. አካል (body):- ህይወታችን ምልዓት እንዲኖራት አካላዊ ጤንነታችን መጠበቅ አለበት። በዚህ ስር ስፖርት መስራት፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ በቂ እረፍት ማድረግ ህመም ካለም መታከምን የመሳሰሉ ክዋኔዎችን መጥቀስ ይቻላል።
3. የስራ ህይወታችን (Job):- ስራ ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ሲግመንድ ፍሮይድ ሁለት አበይት ጉዳዮች ያስፈልጉታል ይላል፤ ስራ እና ፍቅር።
በሌላ አንጻር.. ጤናማ ያልሆነ የስራ አከባቢ ጤናችንን እና ህይወታችንን ማናጋቱ አይቀርም። ስለዚህ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው ስራችን.. አንዱ ሰይፍ መልካም..ሌላው ገጹ ደግሞ ህማም!
4. ማህበራዊ ህይወት:- የሰው ልጅ ማህበራዊ እንስሳ ነው ይባላል። ምንም እንኳን በራስ መተማመን ቢኖረን እና ጠንካሮች ብንሆን..ባንድም በሌላም መልኩ የሌሎችን እገዛ መሻታችን አይቀርም። መቆም ከሌሎች ጋር ነው! ይህም ማህበራዊ ህይወታችን ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከፍቅረኛ፣ ከጎረቤት እና ወዘተ..ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ይመለክታል።
መውጫ:- ከላይ የተያያዘውን ምስል ተመልከቱ። ለሁሉም ማዕዘናት አማካይ የሆነውን መነሻ ዜሮ ብንሰጠው..ከመሃል ተነስተን ለእያንዳንዱ ዕምዳት ከመቶ ነጥብ እንስጥ። ከዚያ ነጥቦችን እናገናኛቸው፤ ነጥቦቹ ሲገናኙ ሚዛኑን የጠበቀ ሮምበስ ሰራ ወይንስ አልተመጣጠነም? ያ ትንሽ ነጥብ የሰጠው አዕምድ ላይ በመስራት ሚዛኑን ለማስጠበቅ እንሞክር።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
“ሁሉም ሰው የየራሱ የህይወት መጽሀፍ ደራሲ ነው”- ሰዐሊ ብሩክ የሺጥላ ከአል ዐይን አማረኛ ጋር ጋደረገው ቆይታ የተወሰደ!
ብዙዎች በትንሽ የህይወት ፈተና በብዙ ተስፋ ሲቆርጡ ይታያሉ አንተ ወደ ፊት እንድትገፋ ወደ ኋላ እንዳትመለስ ያደረገህ ነገር ምንድን ነው?
ብሩክ፡- እኔ ያሳለፍኳቸው ችግሮች እና ፈተናዎች አሁን ለምገኝበት ብርታት ምንጮቼ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
ሰው ትክክለኛ ማንነቱን የሚሰራው ወይም የሚቀርጸው በሚያልፋቸው ፈተናዎች ውስጥ እንደሆነ አምናለሁ፤ እኔም የችግሮቼ እና ፈተናዎቼ ውጤት ነኝ፡፡
እንደምታየው ከእጄ በስተቀር ሌላው የሰውነት ክፍሌ አይንቀሳቀስም። ነገሮች ሁሌም ምቹ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን እኔ ይህን አላስብም፤ ከዚህ ይልቅ ነገ ምን አዲስ ነገር መስራት እችላለሁ በህይወቴስ ውስጥ ምን ለውጥ ማምጣት እችላለሁ የሚለው ጥያቄ ላይ ብዙ ጊዜ አጠፋለሁ፡፡ ዛሬ ላይ በምሰራው ነገር ነገን እንድናፍቅ እና ለነገ እንድጓጓ ያደረገኝ ነገርም ይሄው ነው፡፡
ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ራሴን ከመናቅ እና እንደማልችል ከማሰብ ውጪ ያተረፍኩት ነገር የለም፤ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን መሞከር እና መጣር እንጂ ተስፋ ከመቁረጥ ምንም የሚገኝ ነገር አለመኖሩን በደንብ ተገንዝቢያለሁ፡፡
ሁላችንም ወደዚህ ምድር ያለምክንያት አልመጣንም ወይም ያለ ምክንያት አልተፈጠርንም ሲመስለኝ እርሱን ቁምነገር መረዳት በህይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንድታመጣ የሚያግዝህ ነገር ነው፡፡
በጥረት ውስጥ የምታሳልፈው ዛሬ የምትፈራውን ነገን እንድታነፍቀው ያደርጋል ተስፋ የሚቆርጥ ሰው ባለበት የቆመ ወይም ለችግሮቹ እጅ የሰጠ ሰው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
@melkam_enaseb
የጭንቀት ህመም ስሜቱ ምን ይመስላል?
ወንበር ላይ ተቀምጠህ የወንበሩ የጀርባ መደገፊያ ላይ ጀርባህን አስደግፈህ በአንድ እጅህ የጠረጴዛ ጫፍ ይዘህ የወንበሩን የፊት እግሮች ከመሬት ከፍ አድርገህ ወደ ኋላ ለጠጥ ትላለህ። ለጠጥ ስትል የሆነች ነጥብ ላይ ስትደርስ ልትወድቅ የሚመስል ልብን ስውር የምታደርግ ቦታ አለች። እሷን ስሜት አወካት? Generalized anxiety disorder (የአጠቃላይ ጭንቀት ህመም) ያለባቸው ሰዎች ሁልጊዜ እንደሱ ነው የሚሰማቸው።
ፈተና ልትገባ ስትል ያለው ልብ ቶሎ ቶሎ መምታት፣ ሰውነት መወጣጠር፣ ሀሳብ ብትንትን ማለት...ወዘተ እሱን ስሜት አስታወስከው? GAD ያለባቸው ሰዎች ቀን በቀን የሚሰማቸው እንደዛ ነው። ይሄ ስሜት Apprehensive expectation ይባላል። 'የሆነ አደጋ ሊደርስ እንደሆነ ታውቆኛል' ስሜት ልንለው እንችላለን።
ይሄ ስሜት ለአንድ ቀን ከሆነ ኖርማል ነው። ለሳምንታት ከዘለቀ አሳሳቢ ነው። ለ6 ወራት እና ከዛ በላይ ከቆየ ግን መታከም ያለበት ህመም ነው።
ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከባድ የጭንቀት ስሜት ከተሰማችሁ አቅራቢያችሁ ያለ የአእምሮ ሀኪም ጋር ቀርቦ መታየት ጥሩ ነው። ውጤታማ ህክምና አለው!
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
የአስተሳሰብ መዛነፎች| Cognitive distortions!
እነዚህ የአስተሳሰብ መዛነፎች የድብርት እና ጭንቀት ህመምን ጨምሮ ሌሎች የአዕምሮ ህመሞች ላይ ይስተዋላሉ። ይህ መሆኑ ክስተቶችን አውዳቸውን ባማከለ ሁኔታ እንዳንመዝን ሳንካ ይሆኑብናል። ከራሳችን አልፎ ከሌሎች ጋር ስምምነት እንዳይኖረን ምክንያት ይሆናሉ።
እነዚህን የአስተሳሰብ መዛነፎች በማጤን፡ ሁኔታዎችን በመመርመር፡ ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ በመመዘን፡ በጊዜ ሂደት የተሻለ ሚዛናዊ ሰው መሆን ይቻላል።
ይህን ያማከሉ የስነ ልቦና ህክምናዎች አሉና ባለሞያ ማማከር ብልህነት ነው።
ሚዛናዊ አስተሳሰብ!
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
⬆️ Practice these tips for good mental health!
#WHO
@melkam_enaseb
"አይ ወይም NO" የማለት አስፈላጊነት!
ብዙ ሰዎች “አይሆንም” ወይም NO ለማለት ይቸገራሉ። ይህም ከስብዕናችን ወይም ከአስተዳደግ ሁኔታችን የተነሳ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን "አይ" ማለትን መለማመድ ሰዎች ሊያዳብሩት ከሚችሉት በጣም ጠቃሚ ክህሎቶች ውስጥ አንዱ ነው። በአባባል እንደሚባለው "ጥርጥር ውስጥ ከሆንክ አታድርግ." በተመሳሳይ፣ “አይሆንም” ማለት እንደሚያስፈልግ ሲሰማንም አይሆንም ማለትን መለማመድ አስፈላጊ ነው።
“አይሆንም” ማለት ሆን ተብሎ በሚደረግ ጥረት የሚዳብር ችሎታ ነው። ለመጀመር እነዚህን መንገዶች ይሞክሩ:
1. ህይወትን አይሆንም ከማለት አንፃር መገምገም፡- “አይሆንም” ማለት መጀመር ያለብዎትን የህይወትዎን ቦታዎች ለማሰላሰል እና በወረቀት መፃፍ ትንሽ ጊዜ ይውሰዱ። ከዛም በእያንዳንዱ ሁኔታ "አይ" ማለት ያለውን ጥቅምና ጉዳት መዘርዘር።
2. የሁኔታዎቹን ቅደምተከተል ማዘጋጀት፡- “አይሆንም” ማለት ለእርስዎ በጣም ቀላል ከሆነበት ሁኔታ ጀምሮ ተዋረድ ይፍጠሩ እና ቀስ በቀስ ከቀላሎቹ በጣም አስቸጋሪ ወደሆኑት ይሂዱ።
3. ልምምድ፡- ከሚቀሉት ሁኔታዎች በመጀመር ልምምድ ማድረግ ይጀምሩ። "አይ" ማለትን በትህትና እና በአክብሮት መግለፅ።
"አይ" ማለት ራስ ወዳድነት አይደለም; ይልቁንም ገደብ የማዘጋጀት እና ቅድሚያ የምንሰጠውን ነገር የማስቀደም መንገድ ነው።
ለአእምሮ ጤንነት እና ደስተኛ ሂወት "አይ" ማለት አንዱ አስፈላጊ ነገር ነው። "አይ" ማለትን አጠናክሮ መለማመድ ዛሬውኑ ጀምሩ።
ለማማከር- 0704156858 ይደውሉ ወይም መልክት ያስቀምጡ!
ዶ/ር ይቅናሸዋ ሰለሞን (የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
"ሊያብብ ሲል"
ሱስ ሳይበላው፣ ሲጋራ መግዣ መለመን ሳይጀምር፣ ጉስቁልና ሳያፈዘው፣ ለልብሱ መቆሸሽ ደንታ ቢስ ከመሆኑ በፊት፣ ሰዎችም ሲጣራ ባልሰማ መሄድ ሳይጀምሩ፣ ቃል አባይ ከመሆኑ በፊት፣ ክብሬ ማለት ሳያቆም፣ ለትንሽ ለትልቁ መላክ ሳይጀምር በፊት...ቆንጆ፣ ተወዳጅ እና ዘናጭ ነበር።
ከጓደኞቹ በላይ ድምቅ ያለ ልጅ ነበር፤ የፀጉሩን ፍሪዝ በመስታወት አስር ጊዜ እያየ አስር ጊዜ ያስተካክል ነበር። ሕልመኛ ነበር። እንደ ሁሉም ወጣት ሀብታም መሆን፣ አዋቂ መሆን፣ ቤተሰቦቹን የመርዳት ሕልም ነበረው።
የተንሸዋረረ አራድነት አሳስቶት የለኮሳት ሲጋራ፣ ለሳቅ ብሎ የተጎነጫት አረቄ፣ ለሙድ ብሎ የቀነጠሳት የጫት ቅጠል ስትደጋገም አፈዘዘችው፤ ሕልሙን፣ ወጣትነቱን፣ ክብሩን አረገፈችው።
ማንም ብርቱ ነኝ ቢል ታግሎ የማያስመልሳትን ወጣትነቱን ለማያውቀው ጣዖት እየሰዋት ነው።
ጥግ ላይ ተቀምጦ፤ ዘመን ሄዶ ዘመን በመጣ ቁጥር የሚመጡ ለውጦችን ከዳር በትዝብት እየተመለከተ 'ጊዜው እንዴት ነው የሚሮጠው?' የሚል ይመስለኛል።
"አዎ! እሱ ጋ ያመኛል!'' ከተሰኘው መጽሐፍ..ገጽ-41
(አድኃኖም ምትኩ)
@melkam_enaseb
በቂ እንቅልፍ አለመተኛት የሚያስከትላቸው የጤና ጉዳቶች ምንድን ናቸው?
የሰው ልጅ በመሰረታዊነት ከሚያስፈልጉት ተፈጥሯዊ ዑደቶች መካከል አንዱ የሆነው እንቅልፍ አዕምሮ እና አካል በቂ ረፍት አግኘቶ በሀይል እንዲሞላ ወሳኝ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡
የአውስትራሊያው ፍሊንደርስ ዩኒቨርሲቲ የእንቅልፍ ህክምና ተመራማሪ ሃና ስኮት እድሜያቸው ከ18 እስከ 65 የሆኑ አዋቂዎች በቀን ከ7 እስከ 9 ሰአታት ከ65 አመት በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከ7 እስከ 8 ሰአት መተኛት እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ፡፡
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት 25 በመቶ የሚሆኑ የአለም ህዝቦች በተለያዩ ምክንቶች በእያንዳንዱ ምሽት በቂ እንቅልፍ አያገኙም።
የእንቅልፍ እጦት በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል የእንቅልፍ ሰአት መዛባት፣ የምሽት ፈረቃ ሥራ፣ ልጅ ማሳደግ፣ ሥር የሰደደ ሕመም፣ የእድሜ መግፋት እና ለረጅም ጊዜ ስልክን አብዝቶ መጠቀም ይጠቀሳሉ፡፡
የእንቅልፍ መዛባት ወይም ዕጥረት በአካል እና በአዕምሮ ጤና ላይ ከሚያስከትላቸው የጤና እክሎች መካከል ጥቂቶቹ፦
- የስሜት እና የአዕምሮ ጤና
በአንጎል ውስጥ ያሉ የነርቭ ሴሎች ሲተኙ ጠንካራ አቅም የሚያገኙበትን እረፍት መላበስ ያስችላቸዋል፡፡ ነገር ግን በቂ እና ጥራት ያለው እንቅልፍ ካላገኙ በሚቀጥለው ቀን አዲስ ግንኙነት ለመፍጠር ይቸገራሉ ይህም መረጃን የመገምገም እና የማገናዘብ ችሎታን ይጎዳል።
በዚህ የተነሳ ሰውነትዎ እንደ አድሬናሊን እና ኮርቲሶል ያሉ የጭንቀት ሆርሞኖችን በማመንጨት የብስጭት እና የመነጫነጭ ስሜት እንዲሰማዎት፣ ለውሳኔ እና ለመደምደም ፈጣን እንዲሆኑ እንዲሁም ትዕግስትን በማሳጣት ቁጡ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል።
እንቅልፍ ማጣት የወሲብ ፍላጎትዎን እና መነቃቃትን ሊቀንስ ይችላል፤ በሳምንት ውስጥ በቀን ለአምስት ሰአታት ብቻ የሚተኙ ሰዎች የቴስቶስትሮን መጠናቸው እስከ 15 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ምርምሮች ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም የመንፈስ ጭንቀትን፣ ድብርት፣ ለስሜት መለዋወጥ (ባይፖላር ዲስኦርደር) የመጋለጥ ወይም የማባባስ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም የእንቅልፍ እጦት ለስኳር እና የልብ ህመም፣ ካንሰር፣ ያልተፈለገ ውፍረት፣ የመርሳት በሽታ፣ ዝቅተኛ የማሰላሰል ብቃት እና ሌሎችንም አዕምሯዊ እና አካላዊ የጤና እክሎችን ሊያስከትል እንደሚችል ሳይንስ አረጋግጧል።
Via: Alain Amharic
@melkam_enaseb
ጸጸት የሚያስከትለው የሥነ-ልቦና ጫና!
የቅርብ ዘመዱን መታመም የሰማው አቤነዘር ሄዶ መጠየቅ እንዳለበት ያምናል፤ ነገር ግን በወቅቱ የተጠመደበት ስራ ፋታ ሊሰጠው አልቻለም።
አቤነዘር አስፋው ከአክስቱ ልጅ ጋር የቅርብ ዘመድ ብቻ አልነበሩም የቅርብ ጓደኛሞችም እንጂ። ነገር ግን ከዛሬ ነገ ሲመቻችልኝ እጎበኘዋለሁ ሲል የነበረው አቤነዘር ሳያስበው አስደንጋጭ መርዶ ሰማ።
ሳይታሰብ ጓደኛ እና የአክስቱን ልጅ በሞት ያጣው አቤነዘር “ያኔ እንደ ምንም ሄጄ አለመጠየቄ አሁንም ድረስ ይፀፅተኛል” በማለት ይናገራል።
እንደ አቤነዘር አይነት ወይም በተለየ መልኩ በሚፈጠሩ ክስተቶች በርካታ ሰዎች ጸጸት ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል።
ጸጸት በተደረገ እና ባለፈ ጉዳይ ላይ ትክክል አልነበርኩም ከሚል የጥፋተኝነት ስሜት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሰውኛ የሆነ ስሜት ነው።
ፀፀት ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየት ከፍተኛ ለሆነ የድባቴ ስሜት የሚያጋልጥ እና ነገን እንዳያዩ የሚያደርግ ነው።
ሰዎች ካለፈው ስህተት ከመማር ይልቅ ዛሬም ድረስ የጸጸት እስረኛ ሲሆኑ እና ከራሳቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጤናማ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል ከተቸገሩ ወደ ሥነ-ልቦና ችግር አድጓል ሊባል ይችላል።
ከጸጸት ስሜት ለመውጣትም ያጋጠሙ ችግሮችን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር የተሻለ ሰው ለመሆን እና በዙሪያችን ላሉ ሰዎች የሚጠቅም ነገር ለማድረግ መነሳሻ ሊሆነን ይገባል።
እንዲሁም በሰራሁት ስህተት ምክንያት እኔ መጥፎ ሰው ነኝ ብሎ ከመወሰን ይልቅ የሰራነውን ስህተት ተቀብሎ ትምህርት መውሰድ ጠቃሚ ነው።
ኤርሚያስ ኪሮስ (ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂስት)
Via: WMCC
@melkam_enaseb
ቅናትን መረዳት እና መቆጣጠር እንዴት ይቻላል?
ቅናት በጓደኛሞች፣ በፍቅረኞች እንዲሁም በቤተሰብ መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችል ስሜት ነው።
እንደ አሜሪካ ሳይኮሎጂካል አሶሴሽን (APA) የሳይኮሎጂ መዝገበ ቃላት ፍቺ÷ ቅናት በአሉታዊ የሚታይ ቢሆንም አዕምሯችን ራሱን የሚጠብቅበት ስርዓት ሲሆን አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለመለየት ይረዳል።
በቅናት ዙሪያ ሰፋ ያለ ጥናት ያደረጉት የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዶ/ር ጆሊ ሃሚልተን የሰው ልጆች ከስድስት ወር ዕድሜያቸው ጀምሮ የቅናት ስሜት እንደሚፈጠርባቸው እና ይሄም እያደገ እንደሚመጣ ይናገራሉ።
ይህንን የቅናት ስሜት መረዳት መቻል ራስን ለማሳደግ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሐቀኛ ለማድረግ ይረዳል። ነገር ግን ቅናት ጠቃሚም ጎጂም ነው። በአግባቡ ካልተያዘ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
ቅናትን ገንቢ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አምስት ቁልፍ መንገዶች፦
1. አለመቸኮል- የቅናት ስሜት ሲሰማን በችኮላ አንዳች ነገር ከማድረግ ራስን መቆጠብ ያስፈልጋል። እንዲሁም የተፈጠረውን የስሜት ለውጥ በማወቅ ጉዳዩን ለመረዳት መሞከር ይጠበቃል።
2. ከጥፋት ድርጊቶች መቆጠብ- ከበቀል ወይም ከንዴት የተነሣ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ፤ ለዚህም ደግሞ ቆም ብሎ በጥልቀት በመተንፈስ ስሜትን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው።
3. አለመሸማቀቅ- የቅናት ስሜት የተለመደ በመሆኑ ማፈር አይገባም። ይልቁንም ፍላጎታችንን የሚያስገነዝበን ተፈጥሯዊ ስሜት መሆኑን መረዳት ይገባል።
4. ቅናትን እንደ ፍቅር መገለጫ አለመውሰድ- ቅናት በፍቅር ስሜት ሲገለጽ ጤናማ ያልሆነ ባህሪን ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ፍቅርን በቅናት መልኩ ከማሳየት ይልቅ በግልፅ መነጋገር ይመረጣል።
5. አጋርን ለማስቀናት አለመሞከር- ፍቅራቸውን ለማረጋገጥ ወይንም የትዳር አጋርን ለማስቀናት መሞከር ጎጂ የሆነ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል።
Via: CNN
@melkam_enaseb
ከልጆች ጋር አብረን በምናሳልፍበት ጊዜ ትኩረት ልናረግ የሚገቡን ነጥቦች
1. ልጆችን በራሳቸዉ ቋንቋ / እንደ ህጻን/ ሆነን ማዋራት
ልጆችን በራሳቸዉ ቋንቋ ወይም እንደራሳቸው ሆኖ ለማውራት መፍራት የለብንም፤ በተጋነነ ድምጽና በመዘመር ከልጆች ጋር መግባባት ለልጆች ካዋቂ ንግግር ይልቅ እንደ ህጻን መነጋገርን ልጆች እንደሚመርጡ ጥናቶች ያመለክታሉ፤ ይህም ልጆች ቋንቋን እንዲለዩና የመግባባት ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
2. አብሮ ወጫወት
የልጆች ሀሳባዊ አለም እያደገ ሲሄድ ልጆች መጫወት ይጀምራሉ፣ በዚህ ጊዜ አብሮ ለወጫወት አያመንቱ፣ ልጆች አድገው ወላጆቻቸውን መፈለግ የሚያቆሙበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።
ይህ ከመሆኑ በፊት በተፈጠረዉ እድል በመጠቀም አብሮ በመጫወት ሌሎችን ማክበርን እናስተምርበት፣ ይህን ስናደርግ ለምሳሌ ልጆችን በምናዋራበት ጊዜ የምንሰራውን ስራ አቁመን እነሱን በመስማትና በማየት አኛ ለነሱ ያለንን ክብርና ፍቅር እነሱም ለሌሎች ክብርና ፍቅር እንዲኖራቸው ያደርጋል።
3. ለልጆች መጽሃፍ ማንበብ
ለልጆች መጽሐፍ ስታነቡ ማንበብ አንዱ መዝናኛ እንደሆነ እያስተማሯቾቸው ነው፣ በመጽሐፍ ላይ ያለው ፊደላት ስዕሎች ሁሉ ለልጆች አንዱ የመዝንኛ መንገድ ናቸው፣ በምናነብላቸው ጊዜ የቃላት እውቀታቸው እየጨመረ ይሄዳል።
▪️ለልጆች መጽሃፍ በምናነብበት ጊዜ ልንከተላቸዉ የሚገቡን መርሆች
* በየቀኑ የማንበቢያ ጊዜን ማዘጋጀት፤ ከወክ ቦኃላ ፣ከሻውር ቦኃላ፣ ሊተኙ ሲሉና በጫወታ ጊዜያቸው ሳይሆን እርፍ ባሉበት ሰዐት ብናነብላቸው ይመከራል።
* በማንበቢያ ሰዐታቸው ልጆች ቶሎ ሊሰለቹ ስለሚችሉ አጫጭር ታሪኮችን ብናነብላቸው ሳይሰለቹ ሊሰያዳምጡን ይችላሉ።
* በምናነብላቸው ጊዜ መጽሐፉ ላይ ያለውን ሁሉ በቀጥታ ማንበብ አይጠበቅብንም፣ ረጅም አረፍተ ነገሮችን ማስወገድና ልጆች በሚገባቸዉ ቋንቋ ሊረዱት በሚችሉበት ሁኔታ መግለጽ፣ ድምጽን በመቀያየር ና ስዕላዊ መግለጫ እንዲኖር ማድረግ።
* የማንበቢያ ጊዜውን አዝናኛ ተናፋቂ እንዲሆን ማድረግ፡ የምናነብላቸው መጽሃፍ ስዕላዊ መግለጫ ቢኖረዉ ልጆች ስዕሉን በማየትና በመነካካት ስለሚደሰቱ ጊዜው አዝናኝ ይሆናል።
4. አካላዊ እንቅስቃሴ ከልጆች ጋር አብሮ ማድረግ
የአካል እንቅስቃሴ ለሁሉም የሰው ዘር በሙሉ እጅግ ጠቃሚ ነው፤ ህጻናት በ 6 ወራቸው በእግርና በእጃቸው ሰውነታቸውን መደገፍ ይጀምራሉ ፤ በአጭር ጊዜም እድገታቸው እየጨመረ በመዳህ ለመቀመጥና ለመራመድ ይሞክራሉ።
መዳህ፣ ደረጃ መውጣትና መውረድ ፣ ኳስ መወርወር ፣መሮጥ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ለልጆች ትልቅ ጥቅም አላቸው፣ በነዚህ ሁሉ ወላጆች ለጆቻቸውን በመውደቅና በመነሳት ሊያግዞቸው ይገባል።
5. ከቴሌቪዥን ጋር ያለዉን ቁርኝት መቀነስ
በአሁን ጊዜ ቴሌቪዥን መመልከት የዘወትር ተግባር እየሆነ መጥቷል፣ ይህንንም አብዛኛው ወላጅ ጤናማ እንዳልሆነ ያውቃል፣ በተለይ ከ2 አመት በታች ላሉ ህጻናት በጣም ጎጂ ነው።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ2 አመት በታች ያሉ ህጻናት ብዙ ሰዐት ቴሌቪዥን ላይ የሚያሳልፉ ከሆነ ከሌሎች ከእድሜ እኩዮቻቸው አንጻር ፈጣን አይሆኑም።
ከሰው ጋር ያላቸው ግንኙነት አይፈልጉትም። የቋንቋ እድገታቸው ዝቅተኛ ይሆናል። ትኩረት ማድረግ ይቸግራቸዋል። የእይታ ችግርም ይገጥማቸዋል።
6. ሥርዓት ማስተማር
ልጆች ለራሳቸው ስህተት ኃላፊነት እንዲወስዱ ልናስተምራቸው ይገባል። ጥፋታቸዉን እንዲያስተካክሉና ጥፋታቸውም ውጤት እንዳለው ውጤቱንም መቀበል እንዲችሉ ልናስተምራቸዉ ይገባል።
[BikuZega ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የቀረበ]
@melkam_enaseb
ለመሆኑ Personality ምንድን ነው?
Personality (ባህርይ/ማንነት)፣ ለህይወት/ለራሳችን ያለንን አመለካከት፣ ለሚያጋጥሙን ሁነቶች የሚኖረንን ግብረመልስ፣ አድራጎታችን፣ ከሰዎች ያለንን ተግባቦት፣ ውስጣዊ ስሜትን የምናስተናግድበት አግባብ፣ ውስጣዊ ተነሳሽነታችንን እና መሰል ጉዳዮችን የሚመለከት እና እኛነታችን የሚገለጥበት መለያችን ነው።
ይህ ማንነት አንድም በተፈጥሮ የምንቸረው፤ ሌላም በኑረታችን እየተገነባ የሚሄድ ነው።
የሰው ልጅ ባህርይ/ማንነት እንደየመልካችን አይነተ ብዙ ቢሆንም፤ ጠቅለል አድርገን ብንቃኘው በሚከተሉት አምስት አበይት መለያ ባህርያት ከፍሎ ማየት ይቻላል።
1. Openness to experience:-
አዳዲስ ነገሮችን በማፍለቅ፣ በማጠየቅ፣ በመፈላሰፍ፣ በመመራመር፣ በመራቀቅ፣ ጥበብን በማፍለቅ፣ ውበትን በማድነቅ ይታወቃሉ።
2. Conscientiousness፦
ጥንቁቅ፣ ንቁ፣ በመርህ የሚኖሩ አይነት ናቸው:።
3. Extraversion፦
ግልጽ፣ ነገረ ስራቸው ፊት ለፊት የሆነ፣ ከሰው መቀላቀል የሚሆንላቸው፣ ተጫዋች እና ተግባቢ አይነት ሰዎች ባህርይን ይወክላል።
4. Agreeableness፦
የሌሎች ስሜት ግድ የሚሰጣቸው፣ ሩህሩህ እና ስሜተ ስስ አይነት ሰዎች ባህርይን የሚወክል ነው።
5. Neuroticism፦
ጭንቀታም፣ ስሜታቸውን መቆጣጠር የሚያቅታቸው አይነት ሰዎች ናቸው። ይህ ባህርይ ያለባቸው ሰዎች ለድብርት እና ጭንቀት ህመሞች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው።
ከላይ የተጠቀሱት አምስቱም ባህርይዎች አቻ ተቃራኒ ባህርያት አላቸው።
ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ እናንተን ይገልጣል ብላችሁ የምታስቡት የቱን ነው?
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
የመርሃ ግብር ጥቆማ!
ወርሃዊው የሜንታል ሄልዝ አዲስ መርሃ ግብር ቅዳሜ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም አትላስ አካባቢ በሚገኘው በአዶር አዲስ ሆቴል ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
የዚህ ወር ርዕስም፡- “ናርሲስሲቲክ ፐርሰናሊቲ ዲስኦርደርን መረዳት” የሚል ሲሆን የዚህ ወር እንግዳችን አቶ ጴጥሮስ ሃጎስ ናቸው፡፡
ለመታደም ይህን መስፈንጠሪያ ይጫኑና ይመዝገቡ። https://forms.gle/mNTB3tYLfjXekzPu6
@melkam_enaseb
የስነልቦና ህክምና!
በ Bio-Psycho-Social የህክምና መርህ መሰረት ከአዕምሮ ህመም ህክምናዎች አንዱ የስነልቦና ህክምና ነው።
እንደየ ህመሙ፣ እንደ ችግሩ መንስኤ እና አይነት፣ እንደየ ሰው ስነልቦናዊ ጥንካሬ እና መዋቅር ብዙ አይነት የስነልቦና ህክምና አማራጮች አሉ።
አንድ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር አለ። እሱም የስነልቦና ህክምና የምክር አገልግሎት ብቻ አይደለም። ታካሚው ተመካሪ ብቻ ሳይሆን ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ነው የሚፈለገው። ያው መመካከር ሊኖር ቢችልም ጽንሰሃሳቡ ግን ጠለቅ ያለ እና የራሱ የሆነ አካሄድ ያለው ነው። ታካሚዎች ችግሮቻቸውን እንዲገነዘቡ፣ የልቦና መዋቅራቸውን እንዲፈትሹ እና የመፍትሄ ሃሳቦችን በማመንጨት የተሻለ የልቦና ልዕልና ላይ እንዲደርሱ በሂደት የሚሰራበት የህክምና አይነት ነው የስነ ልቦና ህክምና።
የስነ ልቦና ህክምናዎች ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ እንዲሁም ለአንዳንድ የአዕምሮ ህመሞች ከመድሃኒት እኩል (አንዳንዴም የበለጠ ተመራጭ ሆነው) ሊሰጡ ይችላሉ።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
Vacancy announcement!
Organization: Sitota Mental Health Care & Rehabilitation Center
Position: Psychologist
Quantity: 1
Application Deadline: January 30, 2025
Email to Apply: Sitota.psych.info@gmail.com
@melkam_enaseb
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!
መልካም በዓል!
@melkam_enaseb
Introducing Gize Psychiatric Center: A New Dawn for Mental Health in Addis Ababa!
We are thrilled to announce the opening of Gize Psychiatric Center, a state of the art facility offering comprehensive psychiatric services, designed to see the world "through the patient’s eyes"
Founded by the renowned psychiatrist Dr. Dawit Wondemagegn, the bestselling author of "አለመኖር", Gize Psychiatric Center is dedicated to providing exceptional care with compassion, understanding, and expertise.
Our Services Include:
- Inpatient Care (with the capacity to accommodate up to 80 patients)
- Outpatient Consultations
- Individual and Group Counseling
- Psychotherapy
- Psychiatric Rehabilitation
- Child and Adolescent Assessment
- Addiction rehab
Location: Kotebe Kidanemihret (Meteleya) (Yediro Mekedonia)
https://maps.app.goo.gl/eiu4krDBGxhVsihF8?g_st=com.google.maps.preview.copy
Contact Us Today፡
+251986689565
+251989689565
Through The Patients Eyes, We Find the Path To Healing.
@melkam_enaseb
በልባም ሕይወት ለእርስዎ የቀረበ ራስን የማሳደግ ስልጠና፤ የተሻለ አስተሳሰብ ለተሻለ ስብዕና!
የካቲት 3, 2017 ዓ.ም (Feb 10, 2025) ጀምሮ በሳምንት አምስት ቀን ለአራት ሳምንታት የሚቆይ ስልጠና!
በኒውሮ ሊንጉዊስቲክ ፕሮግራሚንግ (NLP) የተቃኘዉን የ60 ሰዓት የኦንላይን (ዙም) አዕምሮና ስብዕናን የማሳደግ ልዩ የተግባር ስልጠና በመሳተፍዎ የሚከተሉትን እንዲያሳኩ እናግዝዎታለን፡
- ግቦችዎን እና ውጤቶችን ማሳካት እንዲችሉ የሚያግዙ ጠንካራ ሃሳቦችና ልምምዶች
- በሚሰሩት ስራ የበለጠ ትኩረት፣ በራስ መተማመን እና የተሻሉ ውጤቶችን ማግኘት እንዲችሉ
- ስሜትዎንና የአዕምሮ ሁኔታዎን መግራት እንዲችሉ
- ግላዊ ለውጥን ለማሳካት ሁኔታዎችን ከተለያየ አቅጣጫ መመልከት እንዲችሉ ራስዎን ነጻ፣ ችግር ፈቺና መፍትሄ ፈጣሪ እንዲሆኑ
- አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በተሻለ ስነልቦና ለመቋቋም እንዲችሉ
- የሚጎትቱ አመለካከቶችን በማስወገድ በሚያስችሉ የብልጫ አመለካከቶች እንዲቀይሩ
- ወደ ኋላ የሚያስቀሩ ከራስዎ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያደርጓችሁን ግጭቶች በመግራት ወደፊት መጓዝ እንዲችሉ
- ባለፈ ሕይወት ከመዘፈቅና በተያያዝ አሉታዊ ስሜቶች ከመዋጥ ይልቅ የወደፊት ሕይወትዎ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲችሉ
- በሁሉም ደረጃዎች ካሉ ደንበኞች ጋር ጥልቅ ግንኙነትን መፍጠር እንዲችሉ
- ድብቅ አዕምሮዎን በሚፈልጉት መንገድ በመቅረፅ የሚፈልጉትን የህይወት ተሞክሮ በየእለቱ መፍጠር እንዲችሉ ያግዞታል።
ለበለጠ መረጃ ይሄንን ሊንክ በመጫን ልባም ሕይወትን ያናግሩ @libam_hiwot0974
ወይም በቀላሉ በዚህ ሊንክ ይመዝገቡ:⤵️
https://forms.gle/wDEkM5wbeiCSn5Pb7
@melkam_enaseb
የልባም ሕይወት ስልጠና ከሌሎች በምን ይለያል?
1ኛ ስልጠናው በኒውሮ ሊንጉዊስቲክ ፕሮግራሚግ ቴክኖሎጂና ሳይንስ ከ16 ዓመት በላይ ልምድ ባለው ፕራክቲሽነር መስጠታችን
2ኛ የስልጠናው 40% እውቀት 60% የተግባር ልምምድ መሆኑና ትራንስፎርሜሽን (ጥልቅ ለውጥ) ላይ ማተኮራችን
3ኛ በስልጠናው የተሰጡ እውቀቶችንና ቴክኒኮችን መጠቀም የምንችልበትን ስልቶችን የያዘ ማንዋል መስጠታችን
የልባም ሕይወት የ60 ሰዓት የኦንላይን (ዙም) ስልጠና የካቲት 3 ይጀምራል።
- ከምሽቱ፦ 3፡00 - 5፡30
- ለአራት ተከታታይ ሳምንታታ፦ 20 ቀናት
ለበለጠ መረጃ ይሄንን በመጫን ልባም ሕይወት Hi ይበሉ @libam_hiwot0974
ወይም በቀላሉ በዚህ ሊንክ ይመዝገቡ: ⬇️
https://forms.gle/wDEkM5wbeiCSn5Pb7
@melkam_enaseb
በልባም ሕይወት ለእርስዎ የቀረበ ልዩ ስልጠና!
የካቲት 3, 2017 ዓ.ም (Feb 10, 2025) ጀምሮ በሳምንት አምስት ቀን ለአራት ሳምንታት የሚቆይ ስልጠና!
በኒውሮ ሊንጉዊስቲክ ፕሮግራሚንግ (NLP) የተቃኘዉን የ60 ሰዓት የኦንላይን (ዙም) አዕምሮና ስብዕናን የማሳደግ ልዩ የተግባር ስልጠና በመሳተፍዎ የሚከተሉትን እንዲያሳኩ እናግዝዎታለን፡
- ግቦችዎን እና ውጤቶችን ማሳካት እንዲችሉ የሚያግዙ ጠንካራ ሃሳቦችና ልምምዶች
- በሚሰሩት ስራ የበለጠ ትኩረት፣ በራስ መተማመን እና የተሻሉ ውጤቶችን ማግኘት እንዲችሉ
- ስሜትዎንና የአዕምሮ ሁኔታዎን መግራት እንዲችሉ
- ግላዊ ለውጥን ለማሳካት ሁኔታዎችን ከተለያየ አቅጣጫ መመልከት እንዲችሉ ራስዎን ነጻ፣ ችግር ፈቺና መፍትሄ ፈጣሪ እንዲሆኑ
- አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በተሻለ ስነልቦና ለመቋቋም እንዲችሉ
- የሚጎትቱ አመለካከቶችን በማስወገድ በሚያስችሉ የብልጫ አመለካከቶች እንዲቀይሩ
- ወደ ኋላ የሚያስቀሩ ከራስዎ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያደርጓችሁን ግጭቶች በመግራት ወደፊት መጓዝ እንዲችሉ
- ባለፈ ሕይወት ከመዘፈቅና በተያያዝ አሉታዊ ስሜቶች ከመዋጥ ይልቅ የወደፊት ሕይወትዎ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲችሉ
- በሁሉም ደረጃዎች ካሉ ደንበኞች ጋር ጥልቅ ግንኙነትን መፍጠር እንዲችሉ
- ድብቅ አዕምሮዎን በሚፈልጉት መንገድ በመቅረፅ የሚፈልጉትን የህይወት ተሞክሮ በየእለቱ መፍጠር እንዲችሉ ያግዞታል።
ተሳታፊዎችን ያድምጡ: https://www.youtube.com/watch?v=pcIcl1WGEDU
ከአሰልጣኙ ይስሙ: libamhiwot/featured" rel="nofollow">https://www.youtube.com/@libamhiwot/featured
ለበለጠ መረጃ ይሄንን ሊንክ በመጫን ልባም ሕይወት Hi ይበሉ @libam_hiwot0974
ያለው ቦታ ውስን ስለሆነ ፈጥነው ይመዝገቡ!
@melkam_enaseb
#ወቅታዊ
የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ፣ የአእምሮ ጤናና መረዳዳት!
የመሬት መንቀጥቀጥ መሰረተ ልማቶችን፣ ሞቶችን፣ አካላዊ ጉዳቶችን ከማስከተሉ ባለፈ የአእምሮ ጤናን ክፉኛ ሊጎዳዉ ይችላል፡፡ ተጎጂዎች የሰዉ ህይወት ከመቀጠፉ፣ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ የተነሳ ለከፍተኛ ፍርሃትና ጫና ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
በተቃራኒዉ ደግም ሰዎች ተባብረዉ ከቆሙ አደጋ የተሻለ የአእምሮ ጤናና ጫናን የመቋቋም ብቃት ላይ ሊያደርሳቸዉም ይችላል፡፡
ሰዎች የመሬት መንቀጥቀጥና መሰል ድንገተኛ አደጋዎች ሲያጋጥሟቸዉ ለበርካታ የአእምሮ ህመሞች የመጋለጥ እድላቸዉ ይጨምራል፡፡ ጉዳቱ ቀጥታ በራሳቸዉ ላይ ደርሶ፣ በሌሎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ ሲመለከቱ እና አደጋዉ በደረሰበት አቅራቢያ ባይገኙ እንኳ በቅርብ ቤተሰቦቻቸዉ ወይም በጓደኞቻቸዉ ላይ አደጋ እንደደረሰ በመስማት ብቻ ለድህረ አደጋ ሰቀቀን ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
ከአደጋዉ የተነሳ ከቤት ንብረታቸዉ ሲፈናቀሉ፣ በአደጋዉ ንብረቶቻቸዉ ሲወድሙባቸዉ፣ ስራቸዉን ሲያጡ፣ ማህበራዊ ትስስሮች (እድር፣ ማህበር፣ የእምነት ስፍራ…ወዘተ) ሲበጣጠሱባቸዉ ለከፍተኛ ድብርት፣ ለጭንቀት ህመም፣ ለሱስ ህመም፣ ራስን ለማጥፋት አደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡
በተፈጥሮ አደጋ ጊዜ የሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ምልልሶች ይጨምራሉ፤ ሰዎች በአጠቃላይ ደስታን በማጣትና በዘርፋ ብዙ የጤና መቃወሶች ዉስጥ ያልፋሉ፡፡ በሌላዉ ጎን ደግሞ የተፈጥሮ አደጋዎች ሰዎች ህይወታቸዉን ለማቆየት በጋራ የመቆም ዉስጣዊ ግፊታቸዉን በመቀስቀስ በትብብር እንዲቆሙ ሊያደርጓቸዉም ይችላሉ፡፡ ሰዎች ተባብረዉ ሲቆሙና ሲረዳዱ የአእምሮ ጤናቸዉ ይሻሻላል፣ ማህበራዊ ትስስራቸዉ ይጠናከራል፣ ጫናን የመቋቋም አቅማቸዉ ይጎለብታል፡፡
እንደ ማህበረሰብ በቀደመዉ ዘመን የገጠሟቸዉን ጠላቶች በጋራ ተባብረዉ እንደመከቷቸዉ ሁሉ በዚህ ዘመንም የሚገጥሟቸዉን አደጋዎች በመረዳዳት፣ በመተሳሰብና በርህራሄ በመተያየት ሊቋቋሟቸዉ ይችላሉ፡፡
ከአደጋ ጋር የተያያዙ የአእምሮ ህመም ተጋላጭነቶችን ከሚቀንሱ ነገሮች ዋነኛዉ በጉዳቱ ዉስጥ ላለፉ ወይም እያለፉ ላሉ ሰዎች የሚደረግ ማህበራዊ ድጋፍ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ብርቱና መልካም ባህል አለን፤ ባህላችን ሰዉ ለሰዉ መድኃኒቱ፤ ካንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ፤ ሀምሳ ሎሚ ለሀምሳ ሰዉ ጌጡ ለአንድ ሰዉ ሸክሙ እንደሆነ አስቀምጦልናል፡፡ እንደሰዉ ዘር መቀጠላችን የሚወሰነዉ በመተባበራችን ነዉና በዚህ ክፉ ጊዜ ልንረዳዳና ተያያዘን ልንቆም ይገባናል፡፡
አደጋን ታሳቢ ካደረገ እንክንብካቤ መመሪያዎች በመነሳት ባለፍንባቸዉም ሆነ በምናልፍባቸዉ ሰቀቀኖች የሚከተሉትን ነገሮች ብንተገብርና ብንለማመዳቸዉ በብዙ እናተርፋለን፡፡
ደህንነት፦
ሰዎች ዉጤታማ የሚሆኑትና በተሟላ አእምሯዊ ብቃት ላይ የሚሆኑት ደህንነት ሲሰማቸዉ ነዉ፡፡ ደህንነታቸዉ ሲናጋ በፍርሃትና ራስን በማዳን ሩጫ ይጠመዱና የሚጠቅማቸዉን ዉሳኔ አመዛዝኖ መወሰን ያቅታቸዋል፡፡ የሚመለከታቸዉ ሁሉ ከሁሉ በማስቀደም ለሰዉ ልጆች አካላዊ ደህንነት፣ ስነልቦናዊ ደህንነት፣ የስሜት ደህንነት፣ ማህበራዊ ደህንነትና ሞራላዊ ደህንነት መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በማንኛዉም ሁኔታ ዉስጥ ሲኮንና ሲታለፍ ለራስና ለሌሎች ደህንነት ንቁ መሆን የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሆን ይገባዋል!
ታእማኒነትና ግልፀኝነት፦
አደጋዎች ሲኖሩ ብዙ ጥድፊያና ሩጫ መኖሩ የማይካድ ቢሆን የሚከወኑ ተግባራት ሰዎች እምነታቸዉን በሚጥሉበት መንገድ፣ ባልተሸፋፈና ግልፅ በሆነ መልክ ሊደረጉ ይገባቸዋል፡፡ እየሆኑ ስላሉ ጉዳዮች ከሚመለከታቸዉ ተቋማት ወቅታዊ መረጃ ፍሰቱን ጠብቆ መሄድ ይኖርበታል፡፡ እዉነተኛ መታመን እመኑን ከሚል የቃላት ጩኸት ሳይሆን ከተግባር ጥራት ብቻ የሚቀዳ መሆኑን እናስተዉል!
እርስ በርስ መደጋገፍ፣ መተባበር፦
የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ልምድና የጋራ ፈተና ያላቸዉ ሰዎች ህልዉናቸዉ የሚዘልቀዉ በጋራ መተባበርና መደጋገፍ ሲችሉ ነዉ፡፡ በሰዉ ልጅ ኑረት የአንዱ ህልዉና በሌላኛዉ ህልዉና ላይ የተመሰረተ ነዉና ከመገፋፋትና ከመጠፋፋት ይልቅ መደጋገፍን፣ መተባበርን፣ አብሮ መስራትንና መገነባባትን የየዕለት ኑረታችን ማድረግ ግዴታችን ነዉ! ሌላኛዉ ወገናችን ሲሰቃይ ቆመን ካየን ነገ እኛ ስንሰቃይ የሚደርስልን አይኖርም፡፡ እንደጋገፍ! እንረዳዳ! እንተባበር! የተጎዱ ወገኖቻችንን ለማከም ሐኪም መሆን አይጠበቅብንም፤ ለሰዉ መድኃኒቱ ሰዉ ነዉና!
ትህትናና አለመፍረድ፦
ሰዉ እንደመሆናችን ባልገባንና ባልተረዳነዉ ጉዳይ በሌሎች ላይ ጣት ለመቀሰር ልንጣደፍ እንችላለን፡፡ ባህላቸዉን፣ ሀይማኖታቸዉን፣ ታሪካቸዉንና ልዩ ልዩ ልዩነቶቻችንን በማክበር በስቃይ ዉስጥ ከሚያልፉ ሰዎች ልምድ ለመማር መፍቀድና መዘጋጀት እንጂ ከኛ የተለየ ነገር ስለገጠማቸዉ ልንፈርድባቸዉ አይገባንም፡፡ ሰዎች በብዙ ስቃይ ዉስጥ የሚያልፉት ክፉ ስለሆኑ ወይም ፈጣሪ ስለፈረደባቸዉ ሳይሆን ስቃይ የህይወት አንዱ መልክ እንደሆነ እንረዳ፡፡ ከሰዉ ሰራሽ (መደፈር፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ጦርነት፣ ጠለፋ፣ የእሳት አደጋ፣ ግድያ፣ የመኪና አደጋ…ወዘተ) ሆነ ከተፈጥሮ አደጋዎች (ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የመብረቅ አደጋ፣ ረሃብና ድርቅ…ወዘተ) ጫና የተነሳ የሚረበሹ ሰዎችን ስናገኝ ወደ ባለሙያ እንላካቸዉ እንጂ አንፍረድባቸዉ! ማንም ከአደጋና ስቃይ የራቀ አይደለም!
ዶ/ር እሸቱ ጡሚሶ (የሥነ አእምሮ ሐኪም)
(ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ)
@melkam_enaseb