የስራ እና ድርጅታዊ ሳይኮሎጂ ስልጠና!
Certificate Course on Work and Organizational Psychology!
For further details and registration, use the link below! ⬇️
https://forms.gle/L8ghqgECiBp6nQeS9
+25111662437/ +251940200454
(Aha Psychological Services)
@melkam_enaseb
የጆሀሪ መስኮቶች: የማንነታችን አራቱ ክፍሎች!
የጆሀሪ መስኮቶች ከሰው ጋር እንዲሁም ከራሳችን ጋር ያለንን ግንኙነት በተሻለ ለመረደት የሚያግዝ ንድፍ ነው፡፡ ጆሀሪ ስያሜውን ያገኘው ንድፉን በጋራ ከፈጠሩት የስነ ልቦና ባለሞያዎቹ ጆሴፍ ለፍት እና ሀሪንግተን ኢንግሀምን ስም በማቀናጀት ነው፡፡ ማንነታችን በአራት ሊከፈል ይችላል፦ ግልፅ፣ ድብቅ፣ የተሰወረ እና ጨለማ፡፡
ግልፁ ማንነት፦
ይሄኛው ስለራሳችን እኛም ሌላውም ሰው የሚያውቀው ሲሆን ድርጊቶችን፣ እውቀትን፣ ክህሎትን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህኛው ማንነታችን ከሰዎች ጋር ለመነጋገር ችግር የለብንም በተጨማሪም ሰዎች ስለዚህ የማንነታችን ክፍል በሚሰጡት አስተያየት በብዛት እንስማማለን፡፡
ድብቁ ማንነት፦
ይህ ማንነት ራሳችን የምናውቀው ሲሆን ከሌሎች የተደበቀ ነው፡፡ በዚህ መስኮት ውስጥ ያሉ ማንነቶቻችንን ስለምናፍርባቸው ወይም የግል ህይወታችን ስለሆኑ ተጋላጭ እንዳንሆን ከሌሎች እንደብቃቸዋለን፡፡ በተመሳሳይ በትህትና ምክኒያት ሰዎች እንዲያውቁ የማንፈልጋቸው ችሎታዎቻችን እውቀታችንንም ያካትታል፡፡
የተሰወረ ማንነት፦
ይሄኛው ሌሎች ሰዎች የሚያዩት ከኛ ግን የተሰወረው ማንነት ነው፡፡ ምክኒያታዊ እንደሆንን እናስብ ይሆናል ሰዎች ግን ግትር እንደሆንን ነው የሚያውቁት፡፡ ወይም ራሳችንን 'ምንም እንደማያውቅ' ልናስብ እንችላለን ሰዎች ግን በጣም ብልህና አስተዋይ እንደሆንን ሊረዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ መስኮት ውስጥ ነው ሰዎች ቃላችን እና ድርጊታችን እንደሚለያይ የሚያስተውሉት፡፡
ጨለማ (የማይታወቀው) ማንነት፦
ይህ ማንነት በራሳችንም ሆነ በሌሎች የማይታወቅ ክፍል ነው፡፡ ጥሩም ጥሩ ያልሆኑ ሀሳቦች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡
በአጠቃላይ የ ጆሀሪ መስኮቶቸ ራሳችንን ለመረዳት ከዚያም ለማገጎልበት እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያግዝ ንድፍ ነው፡፡
ዶ/ር ዮናስ ላቀው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር
(Autism Spectrum Disorder)
የኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር የአንድን ሰው ማህበራዊ መስተጋብር፣ ተግባቦት እና ባህሪ የሚጎዳ እክል ነው።
እነዚህ እክሎች መለስተኛ፣ ከባድ፣ ወይም መካከለኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር የቡድን ስም ሲሆን በውስጡ አምስት እክሎችን የያዘ ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ባለሙያዎች የሚጠቅሷቸው የኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር አይነቶች አሉ። እነዚህም፦
1.አስፐርገርስ ሲንድሮም (Asperger's Syndrome)
2.ፐርቫሲቭ ዴቨሎፕመንታል ዲስኦርደር (Pervasive developmental Disorder)
3.ኦቲስቲክ ዲስኦርደር (Autistic Disorder)
4.ቻይልድሁድ ዲስኢንተግሬቲቭ ዲስኦርደር (childhood disintergrative disorder)
5. ሬት ሲንድሮም (Rett syndrome) ናቸው።
1. አስፐርገርስ ሲንድሮም
(Asperger's Syndrome)
ይህ የኦቲዝም አይነት ቀለል ያለ የሚባለው ነው። አስፐርገርስ የሆኑ ልጆች በጣም አስተዋይ እና የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ የሚችሉ ይሆናሉ፡፡
- እነርሱ በሚወዷቸው ወይም በተሳቡባቸው ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።
- እነዚህ ልጆች ማኅበራዊ ክህሎታቸው ላይ ተግዳሮት ይገጥማቸዋል።
- በተጨማሪም የንግግር እና ቋንቋ ክህሎታቸው ላይ እምብዛም እክል አይታይባቸውም።
2. ፐርቫሲቭ ዴቨሎፕመንታል ዲስኦርደር (Pervasive developmental Disorder)
- ይህ እክል ከአስፐርገርስ ሲንድሮም ካጋጠማቸው ልጆች የከፋ ሲሆን ነገር ግን ኦቲስቲክ ዲስኦርደር ካላቸው ልጆች የከፋ አይደለም፡፡
3. ኦቲስቲክ ዲስኦርደር (Autistic Disorder)
- ይህ የቆየ ቃል ያለው ከአስፐርገርስ እና ፐርቫሲቭ ዴቨሎፕመንታል ዲስኦርደር የበለጠ እክል ነው፡፡
- ይህም ተመሳሳይ የሕመም ምልክቶችን ያጠቃልላል ግን በጣም ኃይለኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል።
- ይህም የልጆችን ማህበራዊ መስተጋብር፣ ተግባቦት፣ ባህርይ፣ ስሜት እና ጨዋታ የሚጎዳ እክል ነው።
4. ቻይልድሁድ ዲስኢንተግሬቲቭ ዲስኦርደር (childhood disintergrative disorder)
ይህ እክል እጅግ በጣም ከባዱ እና እጅግ የከፋው የስፔክትረም ክፍል እንደሆነ ይገለፃል።
- ይህ እክል ያጋጠማቸው ልጆች በመደበኛነት የሚያድጉ እና ከዚያም ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 4 ባለው መካከል ሲሆን ብዙ ማህበራዊ፣ ቋንቋ እና አእምሯዊ ክህሎቶችን በፍጥነት የሚያጡ ልጆች ናቸው።
- አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ልጆች የሚጥል ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል።
5. ሬት ሲንድሮም (Rett syndrome)
ሬት ሲንድሮም ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር ነው?
ሬት ሲንድሮም ያለባቸው ሕፃናት ብዙውን ጊዜ ከአቲዝም ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ባሕሪዎች አሏቸው። ባለሙያዎቹም ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር መካከል ካሉት ቡድኖች ውስጥ ይመድቡት ነበር፤ አሁን ግን በጄኔቲክ ሚውቴሽን ምክንያት እንደሚከሰት ስለታወቀ በማለት እንደ ASD አይቆጠርም፡፡
በማሕሌት አዘነ
(Speech & Language Therapist)
@melkam_enaseb
ከጎደለን ይልቅ የተሰጠን ይበልጣል!
በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ፖል ሪቻርድ አሌክሳንደር ይባላል። የተወለደው በ1946 ሲሆን በ6 አመቱ በፖሊዮ በሽታ ይያዛል። እንደ ፈረንሳዮች ከ 1952 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በ "ብረት ሳንባ" ማሽን ውስጥ ይኖራል።
ከአንገቱ የላይኛው ክፍል በስተቀር መላ ሰውነቱ ፓራላይዝድ ነዉ። በምስሉ ላይ የምትመለከቱት የመተንፈሻ ማሽን ውስጥ ከገባ ዛሬ 71 አመት ሆኖታል። በዚህ ማሽን ምክንያት ነው በሕይወት ያለው። ከዚያ ለደቂቃ ከወጣ መተንፈስ ስለማይችል በህይወት አይቆይም። የሚያስገርመዉ ግን የህግ ትምህርትን ከታወቀ ዩንቨርስቲ ተመርቆ በህግ ሙያ ያስተምራል።
አንዳንድ ጊዜ የጤንነታችንን እና የሰላማችንን ዋጋ አንረዳዉም። እጅ እግር እያለን በሚረባዉ እና በማይረባዉ ነገር እናማርራለን። ይህ ሰዉ ግን ሁሌም በህይወት በመኖሩ ያመሰግናል።
ከጎደለን ይልቅ የተሰጠን ይበልጣል እና ሁሌም በህይወት በመኖራችን እናመስግን።
(ዶ/ር ኃይለልዑል)
@melkam_enaseb
ከመናገርህ በፊት ሁለቴ አስብ!
ምላስ አጥንት የላትም አጥንት ትሰብራለች የሚለው ንግግር እውነት ነው። ሁሌም ቢሆን ከመናገርህ በፊት አስብ። የምትናገራቸው ቃላት ከድንጋይ በላይ ሰዎችን የማቁሰል አቅም አላቸው። በመናገርህ ተጸጽተህ ይቅርታ ብትጠይቅ ህመማቸውን ትቀንሰዋለህ እንጂ ጠባሳውን አታጠፋውም።
ስለዚህ፦
1ኛ. ስሜታዊ ስትሆን ላለመናገር ሞክር፦
ምክንያቱም ስሜታዊ ስትሆን ምክንያታዊ መሆን አትችልም። ይሄ የአዕምሮህ አሰራር (function) ነው። ስለዚህ ስሜታዊ ስትሆን ለብቻህ ጊዜ ለመውሰድና ራስህን ለማረጋጋት ሞክር። የምትናገረውን ነገር ብታዘገየው የሚፈጠር ተአምር የለም። ከተረጋጋህ በኃላ በችግሩ ላይ ታወራለህ።
2ኛ. የመሰለህ ሁሉ እውነት እንደሆነ አታስብ፦
ስሜት ሀሳባችን የሚፈጥረው ነገር ነው። ሰዎች የበደሉህ ስለመሰለህ በድለውሀል፣ ያጠፋ ስለመሰለህ አጥፍተዋል ማለት አይደለም። ስለዚህ የመሰለህ ሁሉ እውነት እንደሆነ ደምድመህ ከሰዎች ጋር ካወራህ ስሜታዊ ትሆናለህ። ስለዚህ ሁሌም ልክ ነኝ ከሚል መርህ ውጣና ልክ ላልሆን እችላለሁ ብለህ እያሰብክ በመረጋጋት እውነቱን ለማወቅ በሚፈልግ ልብ ጥያቄ ለመጠየቅና ሰዎችን ለመረዳት ሞክር።
ስሜታዊ አለመሆን አትችል ይሆናል። ከስሜት ተነስተህ አለመመለስ (react አለማድረግ) ግን ትችላለህ። ከስሜት ተነስቶ መመለስ ጊዜያዊ ሲሆን መዘዙ ግን የረጅም ጊዜ ነው። አስብበት።
ኤርሚያስ ኪሮስ (ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂስት)
@melkam_enaseb
ጥልቅ ግንኙነት!
ከሰዎች ጋር ብሎም ከ አካባቢያችን ጋር ያለን ግንኙነት ምን ይመስላል?
ውጤታማ በሆኑና ውጤታማ ባልሆኑ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት እንዲፈጠር ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ ከሰዎች ብሎም ከ አካባቢያችን ጋር ያለን ግንኙነት ነው።
የውጤታማ ሰዎች መገለጫዎችና መታወቂያዎች ከሆኑት ነገሮች መካከል ጥልቅ ግንኙነት አንዱና ዋንኛው ነው።
ውጤታማ የሆኑ ሰዎች በግል ህይወታቸው፣ በማህበራዊ ግንኙነታቸው እንዲሁም በስራ ቦታቸው ሰዎችንና አካባቢያቸውን በተሻለ ሁኔታ የመረዳትና የማወቅ አቅምና ጥልቅ መሻት ያላቸው ናቸው።
በዚህም የተነሳ በቀላሉ ከሰዎች ጋር የሚግባቡና የተሻለ ምቹ፣ መተማመን የሞላበት የስራ ሁኔታን በስራ ቦታ እንዲሁም ጥሩ ማህበራዊ ግንኙነቶችን መፍጠር የሚችሉ ናቸው።
ብሎም በግል ህይወታቸው ማሳካትና ማድረግ የሚፈልጓቸውን ነገሮች በቀላሉ እንዲሳኩና ዕውን እንዲሆን በሚደረገው ሂደት ላይ አካባቢያቸውና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ደጋፊዎቻቸውና አጋዦቻቸው ይሆናሉ።
ታዲያ በዙሪአያችን ካሉ ቤተሰቦች ጋር፣ ከስራ ቦታ ባልደረቦቻችን ብሎም በማህበራዊ ህይወታችን ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ምን ይመስላል?
(ዳንኤል አያሌው)
@melkam_enaseb
ይቅርታ እንዴት እንጠይቅ?
ምን ያህሎቻችን ነን ይቅርታ ባለማረግ እና ይቅርታ ባለመጠየቅ ደስታችንን እየቀነስን ያለን?
ይቅርታ እንዴት እንጠይቃለን በሚለው ዙሪያ ትንሽ ለማለት ዳዳው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ሌላውን ሰው አስቀይመው ወይም ጥፋት አጥፍተው ይጸጸታሉ፡፡ ነገር ግን መጸጸትና ይቅርታ መጠየቅ ይለያያሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ይቅርታቸውን ከአንገት በላይ ያደርጉና ተበዳዩን አዛኝ መስለው በከንፈር መጠጣ (lips service) ይሸነግሉታል፡፡ አልያም መልሰው እንደሚያጠፉ እርግጠኛ እየሆኑ እንኳን የይስሙላ ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡
ሺህ ግዜ እያጠፋ ከስህተቱ ለማይማር ሰው ይቅርታ ትርጉም የለውም፡፡ እንዲሁም ይቅርታን ለጥፋቱ መሸሸጊያ የመጨረሻ ምሽግ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሌላውን ሰው ልብ ያደማል፡፡ ይቅርታው በተግባር ለውጥ ስለማይታጀብ ከአፍ አይዘልም፡፡ የዚህ ስሜት በእራሳችን ደርሶ ካላየነው በስተቀር ህመሙ አይሰማንም፡፡ ታዲያ አሳማኝ ይቅርታ እንዴት መጠየቅ ይቻላል?
አንድሪያ ብራንድ የተባለች ሳይኮሎጂስት የሚከተሉት ስድስት ነጥቦች ይቅርታን ለመጠየቅ ጠቃሚዎች ናቸው በማለት ትመክራለች፡-
1. ከልብ የመነጨ ይቅርታ መጠየቅ፡-
የተበዳይ የመንፈስ ስብራት እኛም በግለሰቡ ቦታ ብንሆን ምን ያህል እንደሚሰማን በማሰብ ከውስጥ በመነጨ ስሜት ይቅርታን መጠየቅ፡፡
2. ስለበደሉት ነገር ዕውቅና መስጠትና ዳግመኛ ላለመበደል ኃላፊነትን መውሰድ፡-
ስለአጠፉት ጥፋት እቅጩን መናገር “አውቃለሁ እንዲህ ማድረግ አልነበረብኝም፤ እኔ በእንተ ቦታ ብሆን ምን ያህል እንደሚሰማኝ እረዳለሁ፡፡ እባክህን ይቅር በለኝ!” በማለት ጥፋትን ለማረም ዝግጁ መሆንን ማሳየት፡፡
3. ዳግመኛ ላለመበደል ቁርጠኛ መሆን፡-
የበደላችሁት ሰው ከጥፋታችሁ እንደተማራችሁ እንዲያውቅ ማድረግ፡፡ ይህንንም ዕለት ተዕለት በሚደረግ አግባቦትና ተግባር በግልጽ ማሳየትና ምንም ለውጥ ያላሳየን እንደሆን ወዳጆቻችን በግልጽ ቅሬታቸውን እንዲገልጹ ማድረግ፡፡
4. ይቅርታ የምትጠይቁት ሰው ለእናንተ ምን ያህል እንደሆነ መግለጽ፡-
ከበደላችሁት ሰው ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በማድነቅ መግለጽ፡፡
5. ይቅርታ መጠየቅ፡-
ይቅርታ መጠየቅ በሁለታችሁ መሃል ስላለው ግንኙነት አስፈላጊነት የሚያስረዳ ሲሆን፤ በምላሹ ተበዳይ ይቅርታ ለማድረግ ጊዜን ይፈልግ ይሆናል እንደ ጉዳቱ መጠን፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ሁኔታዎች ይቅር የሚባሉ ነገር ግን በደሉ ሊረሳ የማይችል ስለሚሆን፡፡ “Forgiven but never forgotten” እንዲል የባህር ማዶ ሰው፡፡
6. ለውጥን በተግባር ማሳየት፡-
“የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” እንደሚባለው በአገረኛው ዘይቤ፤ ያጠፉትን ጥፋት ዳግመኛ ላለመተግበር ለእራስ ቃል ታማኝ መሆን፡፡ ይህም የአእምሮ ደውል በመውስጣችን በማቃጨል “እንዲህ ላለማድረግ እኮ እንዲህ ብለህ ቃል ገብተሃል” በተግባር ቃልህን አሳይ ማለት፡፡
በደል ያቆስላል ልብንም ይሰብራል፤ ይቅርታ ግን ቁስልን ይሽራል የተሰበረ ልብንም ይጠግናል፡፡ ይቅርታ እንታረቅ!
መልካም ጊዜ!
(አንቶኒዮ ሙላቱ)
#zepsychologist
@melkam_enaseb
💥ስለ ዳውን ሲንድሮም ማወቅ ይፈልጋሉ?
👉 ዳውን ሲንድሮም ምን ማለት ነው?
👉 ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው?
👉 ተጠቂዎቹን እንዴት መደገፍ እንችላለን?
🗓 በዛሬው እለት ቅዳሜ መጋቢት 9/2015 ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በዳውን ሲንድሮም ላይ በ Clubhouse የምናደርገውን ውይይት ይከታተሉ።
እንግዶቻችን፦
- ዶ/ር ኤርሚያስ ደመቀ
- ዶ/ር ዮሃንስ ግዛው
"ለእኛ ሳይሆን ከእኛ ጋር"
ውይይቱን ለመቀላቀል እዚህ ይጫኑ
ክለብሐውስ ከሌሎዎት ለማውረድ👉 እዚህ ይጫኑ
@melkam_enaseb
⬆️ የአዕምሮ ጤና ምንድን ነው?
ለምንስ ስለ አዕምር ጤና መነጋገር ያስፈልጋል?
አቅራቢ: ፕሮፌሰር አታላይ አለም (MD, PHD)
መቼ: ቅዳሜ መጋቢት 23፣ 2015፣ ከሰዓት 10:00-12:00
የት: አዶር አዲስ ሆቴል
ቦታ ለመያዝ ስምዎትን በጽሁፍ ምልዕክት ይላኩ: 0933616212
@melkam_enaseb
የማይቀርበት ድንቅ ፕሮግራም!
መጋቢት 9/2015 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በካፒታል ሆቴል 'እንዴት ይቅር ልበል' በሚል ርዕስ ተግባራዊ የይቅርታ ህይወት ላይ ያተኮረ ዝግጅት ተዘጋጅቷል::
የእለቱ እንግዶች፦
ዶ/ር ወዳጄነህ መሀረነ
አቶ በኃይሉ ገብረመድኀን
ዶ/ር ተወልደ ገብረእግዚአብሔር (በልጃቸው ሮማን ተወልደ በኩል)
መግቢያ 2ዐዐ ብር
🎯 ዳግማዊ አሰፋ
ስልክ: +251-909-888857
@melkam_enaseb
የ CBT ስልጠና!
ለተጨማሪ መረጃ እንዲሁም ምዝገባ ከታች የተቀመጠውን ሊንክ ይጠቀሙ።
Certificate Course on Cognitive Behavioral Therapy!
For further details and registration, use the link below!
https://forms.gle/XBxigR7BG2EeDc3m6
(Aha Psychological Services)
@melkam_enaseb
ስኬታማ ሴት ልጆችን ለማሳደግ የወላጆች ድርሻ!
በመጀመሪያ ስኬታማ ሴት ማለት ምን ማለት ነው?
- በራሷ የምትተማመን፣ ውሳኔዎች የመወሰን አቅም ያላት፣
- ምርጫዋን የምታውቅና የሌሎችን ምርጫ የምታከብር፣
- ጊዜዋን በዋዛ ፈዛዛ የማታሳልፍ፣ ችግሮችን ለመፍታት የራሷን አስተዋፆ የምታበረክት፣
- ስሜትና ሀሳቧን የምትገልፅ፣ እችላለሁ የሚል አመለካከት ያላት፣
- ራሷን እና ሌሎችን የምታከብር፣ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ የሆነች፣
- ችግር ባጋጠማት ጊዜ ከችግሩ ይልቅ መፍትሔው ላይ የምታተኩር፣
- ለፈጣሪዋ፣ ለባሏ እና ለቤተሰቧ ታማኝ የሆነች፣
- የሴቶች የሆነውን ርህራሄ እና ደግነት ያላት፣
- ራስ በመቻል የምታምን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሌሎችን እርዳታ የምትጠይቅ፣
- ሂወትን እና ዙሪያዋን በአግባቡ የምትረዳ እና ሌሌችን ለመምሰል ጊዜ የማታባክን፣
- በጥላቻ፣ ክፋት እና ሃሜት የሚወረወርባትን ድንጋይ ለውድቀት ምክንያት ሳይሆን ወደከፍታ ለመውጣት ድልድይ የምታደርግ እና ለልጆቿ መልካም አርአያ የሆነች ናት።
ታዲያ እንዲህ አይነት ሴት ለማፍራት ሴት ልጆችን እንዴት እናሳድግ?
1. በዕለት-ተዕለት እንቅስቃሴዋ እኛ እናውቅልሻለን ብለን ለሷ ከመወሰን ይልቅ ራሷ እንድትወስን እድል እንስጣት።
2. በውስጧ ጠቃሚ ነገር እንዳለ ተረድተን እናድምጣት።
3. ብዙ የህይወት እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንድትሳተፍ በማድረግ ከሚያጋጥሟት ችግሮች እንድትማር እና ከስኬቷ እችላለሁ የሚል መንፈስ እንዲኖራት እናግዛት።
4. ሴት ልጅ ማድረግ የምትችለው እና የማትችለው በማለት አንገድባት።
5. ሀላፊነቶች የመወጣት አቅሟ እንዲዳብር ሃላፊነት እንስጣት።
6. ብዙ ለውጪ አለም ሚድያ በተለይ በለጋ እድሜ አናጋልጣት ማለትም ስኬት ውበት እና የአርቲፍሻል ጋጋታ እንደሆነ ለማሳየት ስለሚሞክሩ።
7. እንደ ቤተሰብ ያላችሁን ቤተሰባዊ ባህል አስተምሯት።
8. ራሷን እንድትወድ እና እንድትቀበል እንርዳት ማለትም ውብ እና አስፈላጊ እንደሆነች በፍቅር እንግለፅላት።
9. ከሌሎች ጋር አናወዳድራት፤ ለሌሎች ቀና አመለካከት እንዲኖራት አርገን እናሳድጋት።
10. ያላት ዝንባሌ እንዲያድግ እድል እናመቻችላት።
በመጨረሻም: ችግር ሲያጋጥማት ችግሮቿን እንዴት መፍታት እንደምትችል እናሰልጥናት እንጂ ችግር አጋጠመን ማለት ወድቀናል ማለት እንዳልሆነ ይልቁንም የምንማርበት እድል እንደሆነ እንንገራት።
ሴት ልጆቻችንን እንውደዳቸው፣ እንንከባከባቸው፣ አስፈላጊውን ስልጠና እና ትምህርት እንስጣቸው ደግሞም በነሱ እንደሰት።
መአዛ መንክር (ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት)
#March8
መልካም አለም አቀፍ የሴቶች ቀን!
@melkam_enaseb
#ባለውለታ
"ሰውነት አልሞተም"
በዚህ ግዜ እኛ ኢትዮጵያውያን ብሎም በአለም ላይ የሚታየው የሚሰማው ሁሉ ሰው ሰውነቱን በቃ አጣ? ዓለም ለመኖር አስፈሪ እየሆነች ይሆን? የሚያስብሉ ሰው የሰው ስጋት እየሆነ የመጣበት አስከፊ ነገሮች ተከስተዋል እየተከሰቱም ሰብዓዊነትም እየተሸረሸረ የመጣበት ጊዜ ነው።
ነገር ግን አሁንም በጨለማ ውስጥ ብርሃን የሆኑ እና ለመኖር እንድንጓጓ የሚያደርጉን ጥቂት የማይባሉ ለነብሳቸው ያደሩ ልበ ብሩሃን መልካም ሰዎች ዛሬም አሉ።
ለአብነት ያህል ከሰሞኑ በልበ ብሩሁ ቢኒያም አማካኝነት ለተቋቋመው መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የማስፋፊያ ህንፃ ግንባታው ተጠናቆ ነገር ግን ያላለቁ የበር እና የመስኮት እንዲሁም አንዳንድ የፊኒሺንግ ስራዎች ለማጠናቀቅ የሚውል ገንዘብ አሰባስቤ ሳልጨርስ ከዚች ወንበር ንቅንቅ አልልም ብሎ ራሱን ለመልካምነት አሳልፎ የሰጠውን በበጎ ስራዎቹ የምናውቀው ኮሜድያን ዕሸቱ መለሰን መጥቀስ ይቻላል። እንደዚህ ያሉ መልካም ሰዎች ያብዛልን እያልን፤ ለዚህ በጎ ዓላማ መሳካት ከጎኑ የሆኑ ቅን ልብ ያላቸው መልካም ሰዎች ሁሉ ክብር ይገባቸዋል።
የሀገር ባለውለታው ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ ላደረከው፤ እያደረክ ላለኸው እና ወደፊት ለምታደርገው ሁሉ ክብር ይገባሃል!
"ሰውነት! ሰብዐዊነት አሁንም አልሞተም"
#Bookforall
@melkam_enaseb
#Dailytips
"ሳይገለፁ የቀሩ ስሜቶች አይሞቱም። በህይወት እንዳሉ ተዳፍነው ይከርሙና በአስቀያሚ መልክ ይገለፃሉ።" - ሲግመን ፍሮይድ
@melkam_enaseb
የለውጥ ሂደቶች!
ሰዎች በህይወት ዘመናቸው በተለያዩ የለውጥ ሂደቶች ያልፋሉ። ለውጥ በአንድ ጀምበር አይመጣም ሂደት ነው። ብዙ መውደቅና መነሳቶች፣ ብዙ ተስፋ ሰጪና ተስፋ አስቆራጭ ጊዜያቶች ታልፈው ነው ስኬት ላይ የሚደረሰው። ምናልባት አንዳንዶቹ እድል፣ ብርታት ወይንም ብልጠት በታከለበት ሁኔታ ነገሮች ቶሎ ተፈጽመውላቸው ይሆናል።
እንደ Prochaska እና DiClemente እይታ ከሆነ መለወጥ በሽክርክሪት ይመሰላል።
ለዛሬ ለዚህ ጽንሰ ሃሳብ አስረጂ እንዲሆነን ሱስ የማቆም ሂደትን እንመለከታለን፦
Pre-contemplation/ቅድመ ውጥን:-
በዚህ የለውጥ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎች ስለችግሮቻቸው ያላቸው ግንዛቤ እምብዛም ነው።
ብዙ ሱስ አስያዥ እጾችን የሚጠቀሙ ግለሰቦች፣ ሱሱ በሚታይ ሁኔታ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሰባቸው ቢሆን እንኳን፡ ችግሩን አምኖ ከመቀበል ይልቅ፡ ምንም ችግር እንዳልተከሰተባቸው በመካድ (denial) እና ሱሰኛ እንዳልሆኑና ማቆም ከፈለጉ በየትኛውም ጊዜ ማቆም እንደሚችሉ ሲናገሩ ይስተዋላል። በዚህ ወቅት የባለሙያው ሚና እነዚህን ጉዳቶች እንዲያስተውሏቸው (impact assessment) እጽ ተጠቃሚ መሆናቸው የጠቀማቸውንና የጎዳቸውን ነገር (pros and cons) እንዲዘረዝሩ በማድረግ ነገሮችን እንዲያሰላስሉ መፍቀድ ይሆናል።
Contemplation/ውጥን-
በዚህ የለውጥ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎች ስለ ችግሩ እውቅና ይኖራቸዋል። ንግግሮቻቸው በመለወጥና ባለመለወጥ ሃሳቦች መሃል ይዋልላሉ።
'እጹን መጠቀሜ ከባለቤቴ ጋር እንዳጋጨኝ አውቃለሁ: ግን ደሞ ጓደኞቼን ሳገኝ መጠቀሜ አይቀርም: የክፋ ቀን ወዳጆቼን ማጣት ደሞ አልፈልግም' አይነት ንግግሮች ይስተዋላሉ።
ብዙዎቹ የዕጽ ተጠቃሚዎች እዚህኛው ደረጃ ሲደርሱ ወደ ባለሙያ እርዳታን ለማግኘት የማቅናት እድላቸው ይጨምራል።
በዚህ ወቅት የባለሙያው ሚና ወደ መለወጥ ሃሳቦች እንዲዘነብሉ ማበረታታት ይሆናል።
የችግሩን ግዝፈት እንዲረዱ እና ለውጥ ለማምጣት ብቁ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ በማድረግ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ማሻገር ይቻላል።
Preparation/ የዝግጅት ምዕራፍ
በዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የመለወጥ ውጥናቸው ሚዛን መድፋት ይጀምራል።
Action/ ተግባራዊ የመለወጥ ስራዎች
የለውጥ ስራዎቻቸው መታየት ይጀምራሉ። የሚጠቀሙትን ሱስ መጠን ሲቀንሱ: ከፍ ሲልም ሲያቆሙት ይስተዋላል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ያሉ ሰዎች: የለውጥ ሂደቱን የሚያሳልጡ መሰረታዊ ክህሎቶችን እንዲማሩ ይደረጋል።
Maintenance/ ለውጥን ማስቀጠል
በዚህ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎች: የቀድሞ ባህርያቸው እንዳያገረሽ ስራን ይፈልጋል።
Relapse/ ወደ ቀደመ ባህርይ መመለስ
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደቀደመ ባህርያቸው ሊመለሱ ይችላሉ። እነዚህ ምክንያቶችን መለየትና መስራት መቋቋምያ መንገዶችን መፈለግ ያሻል።
የሱስ ማቆም ህክምናዎች እነዚህን የለውጥ ሂደቶቾን መሰረት አድርገው ይካሄዳሉ።
- በግል ወይንም በቡድን ሊሰጡ ይችላሉ።
- የሱስ ማቆም ህክምናን ለማግኘት የተለያዩ የህክምና ተቋም አማራጮች በመዲናችን ይገኛሉ።
Reference
- Curriculum based motivational group by Ann Fields and Internet
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው
(የአእምሮ ህክምና ሬዚደንት ሃኪም)
@melkam_enaseb
April 2: አለምአቀፍ የኦቲዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ነው!
በኦቲዝም ጥላ ስር የሚኖሩ ልጆች እንድናውቅላቸው የሚፈልጓቸው 10 ነገሮች፦
1. ካለብኝ ኦቲዝም ይልቅ ትኩረታችሁ እንደማንኛውም ልጅ/ሰው መሆኔ ላይ ይሁን።
2. በስሜት ህዋሳት አማካኝነት የማገኛቸው መረጃዎች ከአብዛኛዎቻችሁ በተለየ ሊረብሹኝ ይችላሉ።
3. አንዳንድ ነገሮች እንደተነገሩኝ ወዲያውኑ ላልረዳቸው እና ምላሽ ላልሰጥ እችላለሁ።
4. በየእለቱ በድግግሞሽ የሚደረጉ ነገሮችን መረዳት ይቀለኛል። ድግግሞሽ የምማርበት መንገድ መሆኑን እወቁልኝ።
5. ከሌሎች ልጆች ጋር አታነፃፅሩኝ።
6. እጃችሁን እየጎተትኩ የምፈልገውን የማሳያችሁ በቃላት ሀሳብን እንዴት እንደምገልፅ ስለማላውቅ ነው።
7. ስታስተምሩኝ በቃላት ብቻ ከምትነግሩኝ ይልቅ ብታሳዩኝ እና ብታስነኩኝ በቀላሉ ነገሮችን መረዳት እችላለሁ።
8. ከሚያቅተኝ ነገር ይልቅ የምችለው ላይ አተኩሩ።
9. ከሌሎች ጋር መሆን እፈልጋለሁ ግን እንዴት ማድረግ እንዳለብኝ አስተምሩኝ።
10. ያለምክንያት ውደዱኝ ይገባኛልና።
በመአዛ መንክር (ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት)
@melkam_enaseb
አማራጭ የአእምሮ ህክምና ተቋም- ሴሬኒቲ የአእምሮ ጤና!
ዶ/ር ቢንያም እና ዶ/ር እንግዳ የስነ ልቦና ህክምና ላይ የሚያተኩሩ (Psychologically inclined) የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስቶች ናቸው።
በሴሬኒቲ የአእምሮ ጤና አገልግሎት ማእከል የሚሰጠው የስነ ልቦና ህክምና ሰዎች የተሻለ የአእምሮ ጤንነት እንዲኖራቸው ከማገዝ ባሻገር ትርጉም ያለው እና ደስተኛ ህይወት እንዲመሩ ያግዛል።
በሴሬኒቲ የሚሰጡት አገልግሎቶች፦
- የአእምሮ ምርመራ (Diagnostic evaluation)
- የአስተሳሰብ መግራት ህክምና (Cognitive Behavioural Therapy)
- በስልክ የሚሰጥ የማማከር አገልግሎት (Tele psychiatry)
- በአእምሮ ጤና ዙሪያ ለድርጅቶች የማማከር አገልግሎት (Mental health Consultancy)
አድራሻ: ሽመክት የገበያ ማእከል 10ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 103 ብስራተ ገብርኤል።
ስልክ ቁጥር፡ +251946841200
#Mentalwellness
@melkam_enaseb
ሁላችሁም ተጋብዛችኋል!
"ጥራት ያለው አካቶ ትምህርት ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ሁሉም ህፃናት እና ወጣቶች"
16ተኛው ዓለምአቀፍ የኦቲዝም ግንዛቤ ቀን በድምቀት ይከበራል! ቀኑ በኢትዮጵያ ለ21ኛ ጊዜ በጆይ ኦቲዝም ማዕከል ይከበራል።
ቀን፦ እሁድ መጋቢት 24፥ 2015 ዓ.ም
ሰዓት፦ ከጠዋቱ 3:00- 8፡30 ድረስ፣
ቦታ፦ ሳፋሪ ት/ቤት አካባቢ በሚገኘው ጆይ ኦቲዝሞ ልህቀት ማዕከል ግንባታ ሳይት ላይ።
ስለ ኦቲዝም ያገባኛል!
@melkam_enaseb
⬆️ የጤናወግ በክለብሐውስ!
የአልኮል መጠጦች በጤና ላይ የሚያመጡትን ችግሮች ያውቃሉ?
እሁድ (መጋቢት 17) በ Clubhouse ላይ የአልኮል መጠጦች በጤና ላይ ስለሚያስከትሉት ችግሮች በምናደርገው ውይይት ይቀላቀሉን።
ተጋባዥ እንግዶች፡
ዶ/ር ኃይለሚካኤል ደሳለኝ (የጨጓራ አንጀት እና የጉበት ህክምና ስፔሻሊስት)
ዶ/ር ዮናስ ላቀው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
⏰ ከምሽቱ 12:00 - 2:00 ሰዓት
ውይይቱን ለመቀላቀል እዚህ ይጫኑ
ክለብሐውስ ከሌሎዎት ለማውረድ እዚህ ይጫኑ
@melkam_enaseb
ዳውን ሲንድረም (Down Syndrome) ምንድነው?
March 21: የአለም የዳውን ሲንድርም የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ነው።
በአለም ላይ ከሚወለዱ 800 ህፃናት በአንዱ ህፃን ላይ ዳውን ሲንድረም ሊከሰት ይችላል።
ማንኛዉም ሰዉ ገና በማህፀን ዉስጥ ሲፀነስ 23 ዘረመል ከእናቱ 23 ዘረመል ከአባቱ ወስዶ ሰዉ እንደሚሆን ያውቃሉ?
በሰውነታችን ዉስጥ ያሉ እያንዳንዱ ህዋሶች 23 ዘረመል ከእናት ተጨማሪ 23 ዘረመል ከአባት ወስደው ይሰራሉ። ስለዚህ ባጠቃላይ አንድ ሰዉ 46 ዘረመሎች በእያንዳንዱ ህዋስ ዉስጥ አሉት ማለት ነው።
ሆኖም አልፎ አልፎ ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት በተለያየ ምክንያት ሳይሳካ ሲቀር አንደኛ ዘረመል ቦታ (ላይ ሁለት ከመሆን ይልቅ ሶስት ዘረመሎች ይሆናሉ።
ከ 46ቱ ዘረመሎች በ 21ኛው ዘረመል ቦታ ላይ ሁለት ዘረመል መሆን የነበረበት ቦታ ላይ ሶስት ዘረመል ሆኖ ሲገኝ ዳውን ሲንድሮም (Down syndrome) ያለው ልጅ ሊፈጠር ይቺላል።
ስለዚህ በ አጭሩ ዳውን ሲንድረም ማለት የዘረመል አፈጣጠር ችግር ሲሆን ዘላቂ የሆነ የተለያዩ የጤና እክሎች ሊያመጣ የሚቺል ተፈጥሮ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ከቀላል እሰከ ከባድ ተጓዳኝ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ፦
- የአይምሮ የእድገት ዉስንነት
- የአየር ቱቦ እና አተነፋፈስ ችግር
- የልብ አፈጣጠር ችግር
- የሆርሞን ችግሮች
- የደም ችግሮች
- የአንጀት ችግሮች
Down syndrome ምልክቶቹ ምንድናችው?
ዳውን ሲንድረም ያለበት/ባት ህፃን የሚከተሉት አካላዊ ምልክቶች ይታዩባቸዋል። ለምሳሌ፦
- ጠፍጣፋ እና ለየት ያለ የፊት ገፅታ
- ከፈት ያለ አፍ እና ተለቅ ብሎ የሚታይ ምላስ
- አጭር አንገት
- ዝቅ ያለ ጆሮ
- የአይን ቅድ (አከፋፈት) አቀማመጥ ወደ ላይ ከፍ ማለት
- የአይን ሽፋሺፍት ቆዳ መብዛት
- ደካማ/የላላ ሰውነት ጡንቻ
- አጭር እና ትንሽ መዳፍ
- አጫጭር ጣቶች
- አንድ ወጥ የሆነ የመዳፍ መስመር እና የመሳሰሉት ሊኖሩት ይችላሉ።
አዘጋጅ: ዶ/ር ፋሲል መንበረ (በቅዱስ ጳዑሎስ ሆስፒታል የህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪም እና ረዳት ፕሮፌሰር)
@melkam_enaseb
ባህሪ!
''ባህሪ ሁሉም ሰው የራሱን ምስል የሚያሳይበት መስታወት ነው'' ይለናል ታዋቂው ጀርመናዊው ደራሲና ጸሓፊ ጆሃን ዎልፍ ጋንግ ቮን ጎተ
ከፍላጎቶቻችን አንጻር ምን አይነት ባህሪ ነው በተለያየ ጊዜና ቦታ የምናሳየው?
ባህሪያችን ለሚሰሙን ስሜቶች፣ ለምናስባቸው ሃሳቦች እንዲሁም በአካባቢያችን ለሚፈጠሩ ነገሮችና ሁነቶች በምንሰጠው ምላሽ የተነሳ በዕውን የሚታይና የተገልፀ ማንነታችን ነው።
ታዲያ በሕይወት መንገዳችን ከግቦቻችንና ከዓላማዎቻችን አንጻር ምን አይነት ባህሪ እናሳያለን፣ እናጸባርቃለን?
ግቦቻችንንና ዓላማዎቻችንን ለማሳካት በልበሙሉነት መተግበር የሚገባንን ተግባር መተግበር፣ መክፈል ያለብንን መሰዋትነት በመክፈል ወደ ከፍታው ወደ ግባችን እየተጠጋን ነው ወይስ ከግባችንንና ከዓላማዎቻችን ተቃራኒ የሆኑ ባህሪያትን በማሳየት ፍላጎቶቻችንን እንዳይሳኩ ባለማስተዋል እያጨናገፍናቸው ነው?
ማናችንም ብንሆን በህይወት ሂደት ውስጥ ማሳካት የምንፈልጋቸውን ግቦች ብቻ ማስቀመጥ በቂ አይደለም።
ልናሳካቸው የምንፈልጋቸውን ግቦችና ፍላጎቶች እውን እንዲሆኑ በሂደቱ ላይ የምናሳያቸው ባህሪያት ወሳኝና መሰረታዊ ናቸው።
(ዳንኤል አያሌው)
@melkam_enaseb
ነጻነት ያለው አእምሯችን ውስጥ ነው!
በምስሉ ላይ የምትመለከቱት Ricky Jackson ይባላል። Cleveland, Ohio ነዋሪ ሲሆን ገና በ18 አመቱ በለጋ እድሜው ባልሰራው ወንጀል የሞት ፍርድ ተፍርዶበት 39 አመት ከታሰረ በኋላ (አብዛኛውን ግዜ የሞት ፍርድ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ካላፀደቁት ወደ እድሜ ልክ ይለወጣል)፣ ትክክለኛው ወንጀል ፈጻሚ በመገኘቱ ዳጎስ ያለ ካሳ ተከፍሎት በነፃ የተለቀቀ ሰው ነው።
እናም ልክ ከእስር ቤት ተለቆ ሲወጣ ያሳሰረውን ሰው አገኘውና... «ይቅር ብዬሃለሁ» ....ብሎ አቀፈው።
ቃለ መጠይቅ ላደረጉለት ጋዜጠኞች ደግሞ እንዲ ሲል ተናገረ:-
«እስር ቤት ውስጥ ነህ ማለት እስረኛ ነህ ማለት አይደለም»
ነጻነት ያለው ያላችሁበት ስፍራ ላይ ሳይሆን አእምሯችሁ ውስጥ ነው። የቂምና የጥላቻ እስረኛ እንዳትሆኑ ይቅር በሉ!
ይቅር በሉ፣ መራመድ አታቁሙ፣ ጉዳታችሁ ላይ አትቆዩ! ህይወት ሰፊና ብዙ ጠርዝ ያላት የጉዞ ሃዲድ ናት!
ይቅርታ ለራስ የሚሰጥ ድንቅ ስጦታ ነው። ሰው ይቅር ማለት ሲጀምር ህይወት ይጀምራል።
የበደሉንን ይቅር ማለት መሸነፍ ሣይሆን ፍቅርን ማስተማር፣ ቀናነትን መዝራት፣ ህይወትን ማደስ ነው። #Abrsh
መልካም ቀን!
@melkam_enaseb
ከአምስቱ የስብዕና ሞዴሎች (The Big Five Model) ከሚባሉት የትኛው አይነት ስብዕና ነው ያሎት?
#OCEAN
የመጀመሪያው ተቀባይነት (Openness) የምንለው ነው። ይህ መገለጫ የሚያመለክተው የአንድን ሰው ለአዲስ ሀሳብም ሆነ ክስተቶችን ለመጋፈጥ ያለንን ተቀባይነት ነው። ይህን ስብዕና ለመለካት አንድ ሰው አዲስ ቦታ ላይ በሚሆንበት ጊዜ የሚያሳየውን ምላሽ እና የአዕምሮ አቀባበል ተመልክተን መወሰን እንችላለን።
ጥንቁቅነት (Conscientiousness) የምንለው ሌላኛው የስብዕና አይነት ሲሆን በዋነኝነት ጥንቃቄን ይገልፅልናል። ይህ የሚያመለክተው የአንድን ሰው ድንገታዊ ውሳኔዎችን እና ሀሳቦችን የመቆጣጠር ችሎታ ሲሆን ይህን አድርጎ ምክንያታዊ የሆነ እርምጃን የመውሰድ እና ለስራ ሀላፊነትን የመውሰድ ችሎታን ያመላክታል።
Extraversion የምንለው የአንድን ሰው ከውጫዊው አለም ጋር ወይም ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት መንገድ እና መጠን የምንገልጽበት ሌላኛው የስብዕና አይነት ነው። ከሰዎች ጋር የመቀላቀል ችሎታን እንዲሁም ፍላጎትን እና ከውጪው አለም ጋር ለመገናኘት ያለን ተነሳሽነት በመመልከት ይህን መገለጫ ልናስቀምጥ እንችላለን።
አራተኛው የስብዕና አይነት ተስማሚነት (Agreeableness) የምንለው ነው። ይህ መገለጫ ሌላን ሰው ለመረዳትም ሆነ ለሰዎች ከምናሳየው አክብሮት አንፃር የሚብራራ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሰውን የማመን አቅማችን እና ርህራሄን አጠቃሎ የሚይዝ ነው።
የመጨረሻው የስብዕና አይነት Neuroticism የምንለው ሲሆን እስካሁን ከተነሱት በተለየ መልኩ
አሉታዊ የሆነን ስብዕና የሚያሳይ ነው። ይህን የባህሪ አይነት የተላበሱ ሰዎች እንደ ጭንቀት እና ድባቴ ያሉ አዕምሮን የሚረብሹ ስሜቶች በቀላሉ እና ከፍ ባለ መጠን ይሰሟቸዋል። #APS
@melkam_enaseb
ውድቀታችን የኑረታችን መጨረሻ አይደለም!
ሁሉንም ነገር ከልብ ከፈለግነው ያደክመናል እንጂ አናጣውም። ከልቡ የፈለገ ሰው የልቡን አያጣም።
ሽንፈቶቻችን ሁሉ በጥረቶቻችን ይሸነፋሉ። ድክመቶቻችንም በጥንካሬአችን ይደመሰሳሉ። በማይቆም ጥረት ውስጥ ስንኖር ለማይቀር ድል እንታጫለን።
የምንኖረው መሆን እና አለመሆን በሚፈራረቁባት ምድር ላይ በመሆኑ ለደቂቃም ቢሆን ጥሮና ግሮ ከመኖር አንታቀብ። ብዙ ነገር ሊያጥረን ይችላል ነገር ግን የሁሉም እጥረቶች ማጥፊያ ራሱ ጥረት ብቻ መሆኑን አንርሳ።
ከተጋን እየፈካን እንኖራለን። ትጋታችን ምኞታችንን ከተረትነት ይታደገዋል። ሳንሰለች ከታገልን የፈለግነው ሁሉ እኛን ይፈልገናል።
በከፈለኝ ዘለለው ['አሞዛ']
መልካም ቀን!
@melkam_enaseb
⬆️ You are invited to join a Zoom webinar!
When: Wed, march 15, 2023 at 12:00 Pm.
Topic: Management of Schizophrenia especially on the newly imported drug Paliperidone.
Join Zoom Meeting: https://us05web.zoom.us/j/4284924927?pwd=QjV1aWhxUnV1REQrcUJqdjdrUzFXZz09
Meeting ID: 428 492 4927
Passcode: sitota
@melkam_enaseb
ስብዕና!
"ከህመሞች ሁሉ ትልቁ ህመም ካንሰር ወይም ኤድስ ሊመስለን ይችላል። እውነቱ ግን ከስብዕና መዛባት የከፋ ህመም የለም። ውጫዊ መልክ የሠው የገጽ ሽፋን ነው። ስብዕና ግን የሠው እውነተኛ መልክ ነው። በየዕለቱ አብረን የምንኖረው ሰው ቢኖር፣ እውነተኛና የማያረጅ ዘላቂ ማንነታችን ሰብዕናችን ነው። በዓይናችን የማናየው እውነተኛ መልካችን በውስጥ ማንነታችን ውስጥ ተቀብሮ ያለው ሰብዕናችን ነው። የሰብዕና ስንኩልነት፣ ጠባሳዎችና መዛባቶች ቤት ያፈርሳሉ፣ አገር ይንዳሉ፣ ግንኙነትን ይመርዛሉ። ለማከም ለማዳን ብቻ ሳይሆን ለማየትና ህመሙን ለመረዳትም አዳጋች ነው።
ሰብዕና በልጅነት እንደ ተቦካ ሲሚንቶ፣ በአዋቂነት ደግሞ እንደ ደረቀ አርማታ ነው። የብዙ ሠው ሰብዕና እንደ ተቦካ ሲሚንቶ በልጅነት ጊዜ በትክክል የሚቀርፀው ካለገኘ ተንሻፎና ተዛብቶ ያድጋል። ዕድሜው ከገፋ በኋላ ደርቆ ስለሚጠነክር፣ ብዙ ጊዜ ለመከራ መዶሻና ለምክር መጥረቢያ አዳግቶት አገር ያጠፋል። የልጅ ውበቱ በቀላሉ መሰራቱ... ያዋቂ ክፋቱ ለመለወጥ አስቸጋሪ የሆነ ክፉ እውቀቱ ነውና።"
(''ሌላ ሰው'' መጽሐፍ በዶ/ር ምህረት ደበበ)
@melkam_enaseb
"ለምን እኔ ብቻ?" እያልክ ትጠይቅ ይሆን?
እኩዮቼ አግብተዋል።
እኩዮቼ ልጆች አፍርተዋል።
እኩዮቼ ጥሩ ሥራ ይዘዋል።
እኩዮቼ ስኬት ተጎናጽፈዋል።
እኩዮቼ ውድ ቤትና መኪና አሏቸው።
እኩዮቼ በማኅበረሰቡ የተከበሩ ናቸው።
እኩዮቼ እንዲህ ናቸው፤ እንዲያ ናቸው...
እያልክ ይሆናል።
ትክክል ብለሃል። ይሁንና ጨርሰህ መርሳት የሌለብህ...
ከሚታየው ምቾት ባሻገር የማይታዩ ብዙ ሸክሞች። ከሚማርኩ ፈገግታዎች ጀርባ ብዙ የልብ ቁስልና ህመሞች እንዳሉ እወቅ።
ከሩቅ ያማረ ኑሮ ሁሉ የስኬት ምልክት፣ ከውጭ የሚታይ አንጸባራቂ ነገር ሁሉ ወርቅ አይደለምና። ስለዚህ ያወቅነው 'ደስታውን' ሲሆን ያላወቅነው ደግሞ 'ጉድለቱን/ችግሩንና ድካሙን/' ነው።
እኩዮችህ ሆነው በህይወት የሌሉትን።
እኩዮችህ ሆነው በህመም የሚሰቃዩትን።
እኩዮችህ ሆነው በአእምሮ መታወክ በማህበረሰቡ እንደ እብድ የተቆጠሩትን።
እኩዮችህ ሆነው መንገድ ዳር የሚያድሩትን።
እኩዮችህ ሆነው ወላጅ አልባ የሆኑትን።
እኩዮችህ ሆነው የለት ጉርስ ያጡትን።
እኩዮችህ ሆነው አንተ የምትኖረውን ኑሮ የሚናፍቁና ባንተ ህይወት የሚቀኑ መሰል የሰው ዘርን...ረስተሃል።
ምናልባት የምትፈልገው ስፍራ ላይ አልተቀመጥክ ወይም የምትመኘውን ነገር አላገኘህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከብዙዎች በላይ ደስተኛ ነህ። ስለዚህም ፈጣሪህን ባለህ ነገር አመስግን።
አንተ ለብቻህ የሆነብህ ነገር የለም። አንተ ጋር የጎደለህን ሌላው ጋር ስታይ 'ሁሉ የሞላለት' መስሎህ ነው። ባወቅኸው ልክ የሰውን ህይወት አትመዝን፣ የራስህንም አታቃል። ያወቅክ የመሰለህ ያላወቅኸው ብዙ አለና። ስለዚህ በምንም አይነት የህይወት ትግል ውስጥ ብትሆን ደስታን ምርጫህ አድርግ። ሰላምንም ውደዳት። ሁልጊዜም በፈጣሪህ ደስ ይበልህ!
(Samuel Geda)
@melkam_enaseb
ከቀዳዳ ጀልባ ላይ ውሀ በማንኪያ!
አማኑኤል ሆስፒታል በሀገራችን ብቸኛው የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነው። ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ አልጋዎች አሉት። በተመላላሽ ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ወደ አርባ ክፍሎች አሉት።
የአእምሮ ህመም ከ5 ሰው 1 ሰው ላይ ይከሰታል። በሀገራችን ያለው የአእምሮ ህመም ስርጭት (Life time prevalence) 27% ነው። የሀገራችን ህዝብ 120 ሚልየን ይገመታል። ያ ማለት 30 ሚሊዮን ህዝብ በአንድ ወይም በሌላ ወቅት የአእምሮ ህመም ያጋጥመዋል ማለት ነው። በሚያሳዝን መልኩ አብዛኞቻችን የአእምሮ ህመም የሚመስለን ልብሱን አውልቆ ጎዳና የወጣ ሰው ነው። የአእምሮ ህመም ማለት ህፃናት ላይ የሚከሰት ትኩረት ያለማድረግ ችግር (ADHD)፣ መኮላተፍ (Fluency disorders)፣ ከ5አመት በኋላ አልጋ ላይ መሽናት (enuresis)፣ በአስራዎቸ እድሜ የሚከሰቱ የስሜት መዋዠቅ፣ የድብርት ህመም (Depression)፣ ሱስ፣ የእንቅልፍ ችግር (Insomnia)፣ የወሲብ ፍላጎት አለመኖር (Hypoactive sexual desire disorder)፣ በእድሜ ማምሻ ላይ የሚከሰት የመርሳት ህመም (Dementias) .....ወዘተ ማለት ነው።
የአእምሮ ህመም በሁሉም ክልሎች ይከሰታል። ገጠርና ከተማ፣ ብሄርና ሀይማኖት አይለይም። ከአእምሮ ህመም ስርጭት አንፃር አንድ አማኑኤል የሚሰጥ አገልግሎት ከቀዳዳ ጀልባ ላይ የሞላውን ውሀ በማንኪያ እንደመድፋት ነው። ትልልቅ የአእምሮ ህክምና ተቋማት ቢቻል በየዞኑ ባይሆን በየክልሎች ያስፈልጋል። 27% ማለት ሁላችንም ቤት ያለ ጉዳይ ማለት ነው።
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው
@melkam_enaseb