Schizotypal Personality disorder
ከ Cluster A የስብዕና መዛነፎች (Paranoid, SCHIZOTYPAL እና Schizoid) አንዱ ነው።
እንደሌሎቹ የስብዕና መዛነፎች ሁሉ ይህም የስብዕና መዛነፍ ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት ከጉርምስና እድሜ ጀምሮ ነው።
መገለጫዎቹ:-
1. ሁኔታዎች በሙሉ እነሱ ላይ እንዳነጣጠሩ ይሰማቸዋል፤ ሰዎች ሁሉ ስለነሱ የሚያወሩ ይመስላቸውና ይረበሻሉ።
2. ወጣ ያሉ አስተሳሰቦችን በማራመድ ይታወቃሉ። ወጣ ላሉ ፍልስፍናዎች፣ የሴራ ትርክቶች (Conspiracy theories)፣ telepathy እና ስድስተኛ የስሜት ህዋስ ላሉ ጉዳዮች ትልቅ ቦታን ይሰጣሉ። የሰዎችን ስሜት ማንበብ እና ነገሮችን ቀድመው መረዳት እንደሚችሉ፣ የሌሎችን እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ችሎታ እንዳላቸው ሲናገሩ ይስተዋላል።
3. ወጣ ያሉ ባህርያትን ያራርምዳሉ:- ለምሳሌ ወጣ ያሉ፣ አብረው የማይሄዱ እና ከማህበረሰብ ባህል ያፈነገጡ አለባበሶች ሲለብሱ ይስተዋላል።
4. ስሜት ህዋሶቻቸው የሌለን ነገር እንዳለ አድርገው፣ ያለን ነገር ደግሞ አዛብተው ይረዳሉ።
5. ንግግራቸው ለመረዳት የሚያስቸገር ሲሆን፣ ወጋቸውን በአጭር ከመቋጨት ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም መሄድ እና ከልክ በላይ ማብራራት ይቀናቸዋል።
6. ሲበዛ ተጠራጣሪዎች ናቸው፣ ፊታቸው አይፈታም።
7. ብቸኞች ናቸው፤ ሰዎችን ለመቅረብ ይቸገራሉ። ከቅርብ ዘመዶቻቸው ሌላ የሚቀርቡት ወዳጅ አይኖራቸውም። ይህም የሚሆነው አንድም ከተጠራጣሪነታቸው፣ ደግሞም የተለየን ነን ብለው በማሰባቸውም የተነሳ ነው። ሰዎች ጋር ተቀላቅለው በቆዩ ቁጥር የመረበሽ ስሜታቸው ከመቀነስ ይልቅ ይጨምራል፣ ጥርጣሬያቸው ስለሚያይል።
በነገራችን ላይ:- ይህ የስብዕና መዛነፍ በ Schizophrenia spectrum and other psychotic disorders ውስጥም የሚካተት ነው።
ህክምናው:- የስነልቦና ህክምና እና መድሃኒት (በተለይም የጸረ-ሳይኮሲስ መድሃኒቶች) የሚታዘዙ ይሆናል።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
'ምን ሆኛለሁ?' መፅሀፍ!
የስነ ልቦና ባለሞያዋ ትዕግስት ዋልተንጉስ እና ጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ የተጣመሩበት 'ምን ሆኛለሁ?' መፅሀፍ!
አንዳንድ ጊዜ የማትፈልጉትን ነገር ስታደርጉ ራሳችሁን ታገኙታላችሁ። አንዳንድ ጊዜ የምታደርጉት ድርጊት ራሳችሁን የሚጎዳ ይሆናል። ይሄኔ 'ምን ሆኛለሁ?' ትላላችሁ። መልሱ የሚገኘው ወደ ልጅነት ሄዶ የስነ ልቦና ውቅርን በመመርመር ነው።
የምታደርጉት ድረጊት ግራ አጋብቷችሁ 'ምን ሆኛለሁ?' ብላችሁ ከጠየቃችሁ ይሄ መፅሀፍ ልጅነታችሁን በመመርመር ራሳችሁን በተሻለ እንድትረዱ ያግዛችኋል።
መፅሃፉን ገዝታችሁ እንድታነቡት እንጋብዛለን!
@melkam_enaseb
የመርሃ ግብር ጥቆማ!
ወርሃዊው የሜንታል ሄልዝ አዲስ መርሃ ግብር ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም አትላስ አካባቢ በሚገኘው በአዶር አዲስ ሆቴል ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
የዚህ ወር ርዕስም፡- “A Journey to Deal with Secondary Trauma of Health Professionals and Gender-Based Violence Survivors” የሚል ሲሆን የዚህ ወር እንግዳችን ዶ/ር ሰብለ ሃይሉ ናቸው፡፡
ለመታደም ይህን መስፈንጠሪያ ይጫኑና ይመዝገቡ። https://forms.gle/gMnmRBBSfhR7YyYB6
@melkam_enaseb
እራስን ከአዕምሮ ህመም መጠበቂያ መንገዶች ምንድን ናቸው?
ለራስ መደረግ ያለበት ጥንቃቄ እንዴት ያለ ነው?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአእምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህርና ሀኪም እንዲሁም የስጦታ የአእምሮ ህክምና እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዮናስ ባህረ ጥበብ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ማብራሪያ ይህንን ማስፈንጠሪያ በመጫን ያድምጡ: ➡️ https://tinyurl.com/msuxf9zj
Via: ሸገር ኤፍኤም
@melkam_enaseb
ሳይኮሲስ ምንድን ነው?
እንትና እኮ 'ሳይኮቲክ' ነው ምናምን ብላችሁ ወይንም ሰምታችሁ ታውቃላችሁ ብዬ አስባለሁ።
ለመሆኑ አንድ ሰው ሳይኮሲስ አጋጠመው የሚባለው መቼ ነው?
በመጀመርያ ሳይኮሲስ ማለት ምን እንደሆነ ትርጉሙን እንመልከት፦ ሳይኮሲስ 'እውነታን በአግባቡ አለመረዳት' እንደማለት ነው። እውነታ ምንድን ነው? እስቲ ተፈላሰፋበት።
ለአሁኑ ግን እውነታን እንዲህ እንፍታው እና ወጋችንን እንቀጥል:- እውነታ በስሜት ህዋሶቻችን በኩል የሚቃኝ (ማለትም የሚታይ፣ የሚሰማ፣ የሚዳሰስ፣ የሚሸተት እና የሚቀመስ) እና በአዕምሯችን ትርጉም የሚሰጠው ክስተት (Stimuli) ነው።
ሰዎች ሳይኮሲስ ሲያጋጥማቸው አዕምሯቸው የሌለን ነገር እንዳለ አድርጎ ትርጉም መስጠት ይጀምራሉ።
1. ሃሉሲኔሽን
- ለሌሎች የሚታይ ነገር ሳይኖር እንደታያቸው (Visual Hallucinations)
- የሚሰማ ነገር ሳይኖር ድምጽ እንደተሰማቸው (Auditory Hallucination)
- የሚሸተት ነገር ሳይኖር የሆነ ነገር እንደሸተታቸው (Olfactory Hallucination)፣
- በቆዳቸው ላይ ለየት ያለ እንቅስቃሴ እንደሚሰማቸው (Tactile Hallucination)
2. ዴሉዥን
ለየት ያለ እና ከእውነታው ያፈነገጠ አስተሳሰብ ማራመድ ይጀምራሉ። እሳቤያቸውን በሙሉ እርግጠኝነት የሚያምኑበት ሲሆን ከሚኖሩበት ማህበረሰብ/ባህል አስተሳሰብ ጋርም አብሮ የሚሄድ አይደለም። ይህ ዴሉዥን ይባላል።
ለምሳሌ:-
- ይከታተሉኛል፣ መተት አሰርተውብኛል አይነት ጥርጣሬ (Persecutory delusion)
- ያልሆኑትን እንደሆኑ እና የተለየ ችሎታ/ጸጋ እናዳላቸው አድርገው ራሳቸውን መካብ (Grandiose Delusion)
- ምክንያት አልባ ቅናት (Delusional Jealousy)
- በሆነ አካል ቁጥጥር ስር እንዳሉ ማሰብ (Delusion of control)
- አንዳንድ መደበኛ ክስተቶችን ለነሱ የተለየ መልእክት እንዳላቸው ማሰብ (delusional perception) እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
በነገራችን ላይ ሳይኮሲስ በዋነኝነት ከ ዶፓሚን ስርአት መዛባት ጋር ተያይዞ እንደሚመጣ ይታመናል። ይህን መዛባት የሚያመጡ ብዙ ምክንያቶች አሉ።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
የእንቅልፍ ማጣት ችግር
እንደ ተመራማሪዎች ገለጻ እንቅልፍ ለአዕምሮ ንቃት እና ብርታት አስፈላጊ መሆኑ ይነገራል።
ሥራን በአግባቡ ለመስራት፣ ማህበራዊ ኑሮን ለማመጣጠን እንዲሁም ጤናማ ሆኖ ለመቆየት ጥሩ እንቅልፍ ወሳኝ መሆኑም ይታወቃል።
አይናችንን ከድነን ለመተኛት መቸገር ወይም በአግባቡ አለመተኛት ደግሞ ከድካም በዘለለ የጤና እክሎች ያስከትላል።
የእንቅልፍ ማጣት ችግር ምንድን ነው?
እንቅልፍ ተፈጥሯዊ የሆነ ሂደት ነው በቀን ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆነውን በእንቅልፍ ነው የምናሳልፈው፡፡
ታድያ ሰዎች ባላቸው የእለት ተዕለት መስተጋብር አንዳንዴ ለመተኛት ምቹ የሚሆኑ ጊዜያቶች ይኖራሉ አንዳንዴ ደግሞ ሳንተኛ እና በቂ እንቅልፍ ሳናገኝ ልንነቃባቸው የምንችላቸው ሁኔታዎቸ አሉ፡፡
ከብዙ የአእምሮ ጤና መዛባት ጋርም የእንቅልፍ ማጣት እንደ ምልክት ሆኖ ሊመጣ ይችላል፡፡
መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው?
- የውጥረት መጠን መጨመር
- እየጠጡ ማምሸት
- ስልክ እና ኮምፒውተር ላይ እረዥም ሰዓት ማሳለፍ
- ሰው ሰራሽ የሆኑ ክስተቶች (ጦርነት፣ ግጭት)
- ተፈጥሯዊ የሆኑ አደጋዎች (ጎርፍ፣ ረሀብ፣ ድርቅ) ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች አዕምሯቸው ላይ የሚፈጥረው ጠባሳ እንቅልፍ ሊያሳጣቸው ይችላል፡፡
ምን ሊያስከትል ይችላል?
- ቀን ላይ የሚኖረን ንቃት እና ትኩረት መቀነስ
- ድካም ድካም ማለት
- ከባድ የሆነ የአዕምሮ ጤና መታወክ
- የሀይል መቀነስ
- መበሳጨት
- ከሰዎች ጋር ለመግባባት መቸገር
- የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም መቀነስ
- መቆጣት
- የማድመጥ አቅማችን ማነስ
- አዕምሯችን ላይ የሚፈጥረው እረዥም ግዜ የሚቆይ ተፅእኖ ደግሞ ለሌሎች አካላዊ ህመሞች ሊያጋልጠን ይችላል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ ምን ማድረግ ይመከራል?
- የሚረብሸን ነገር ካለ የቅርብ ለምንለው ሰው ማማከር
- የሚያሳስቡን ነገሮች ሲኖሩ መፃፍ
- የስነ ልቦና ባለሙያዎችን ማማከር
- ሙቅ ሻወር መውሰድ
- የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ
- ትኩስ ወተት መጠጣት
- ለእንቅልፍ የሚሆን ሁኔታ ማመቻቸት (ሲተኙ ከ100 ጀምሮ ወደኋላ ቁጥር እየቆጠሩ መተኛት)
- የቀን ልምዳችንን መጠበቅ (ተመሳሳይ ሰዓት መተኛት እና መንቃት) ይጠቀሳሉ፡፡
ቴድሮስ ድልነሳው (የስነ-ልቦና ባለሙያ)
@melkam_enaseb
የማህበራዊ ጭንቀት/ፍርሃት (Social Anxiety Disorder) or Social Phobia - ህክምና
የማኅበራዊ ጭንቀት/ ፍርሃት ሁለት አይነት ህክምና አሉት። እንዚህም የስነ-ልቦና ህክምና እና የመድሃኒት ህክምና ናቸው። የህክምናው ምርጫ የሚወሰነው የሚከተሉትን ታሳቢ በማድረግ ነው።
- ማኅበራዊ ጭንቀቱ በተጠቂው ግለሰብ ለይ በሚፈጥረው የህይወት ጫና፣ ክብደት፣
- የታካሚ ምርጫ እና ተነሳሽነት፣
- የታካሚው በሕክምናው ውስጥ የመሳተፍ ችሎታ፣
- ተጓዳኝ የአእምሮ ሕመሞች ካሉ፣ ወዘተ...።
የስነ-ልቦና ህክምና
የኮግኒቲቭ-ቢሄቪየር ህክምና (Cognitive and behavioral Therapy) ዉጤታማ የህክምና አይነት ሲሆን፤ አስተሳሰብ እና ባህሪን በመቀየር የሚሰራ የንንግር ህክምና አይነት ነው።
ህክምናው ጊዜ የሚፈልግ እና ፍርሃትን በመጋፍጥ የሚደረግ የህክምና አይነት ነው። የግለሰቡን ተነሳሽነት የሚጠይቅ ሲሆን በደንብ ከተሰራ አመርቂ ዉጤት ያመጣል። ህክምናው በግለሰብ ወይም በቡድን ሊስጥ ይችላል።
የመድሃኒት ህክምና
የተለያዩ የመድሃኒት አይነቶችን በመጠቀም የማኅበራዊ ጭንቀትን ማከም ይቻላል፤ ዉጤታማ ለውጥም ያመጣሉ። በተለይ ተጓዳኝ የአዕምሮ ችግሮች ካሉ እና በአፋጣኝ ለውጥ ካስፍለገ ይህ ህክምና ተመርጭ ይሆናል።
ስር ለሰደደ የጭንቀት ህመም የህክምና ውጤት ጊዜ የሚወስድ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። በርካታ ሳምንታት ወይም ወራቶችን በስነ-ልቦና ህክምና ሲያሳልፉ እንዲሁም ለእርስዎ ሁኔታ ትክክለኛውን መድሃኒት እስከሚገኝ ድረስ የተወሰነ የሙከራ ጊዜ ቢፈጅም፤ እምርታዊ ጉዞው በስተመጨረሻ ለውጥ ያመጣል።
ዶ/ር መሀመድ ንጉሴ (ሳይካትሪስት)
@melkam_enaseb
ስለ አለኝታ ምን ያህል ያውቃሉ?
6388 አለኝታ ነጻ የስልክ መስመር ላይ ይደውሉና ስነልቦናዊ ድጋፍ ያግኙ።
@melkam_enaseb
የካርል ዩንግ ጥልቅ የፍልስፋና እና ሥነልቦናዊ ንግግሮች!
1. ”ባንተ በራስህ ውስጥ ያለዉን ጨለማ ማወቅ በሌሎች ጨለማ ላይ ለመስራት መንገዱን ይጠርግልሀል”
2. ”ንቁ ባልሆነዉ የአእምሮህ ክፍል ተቀምጠው ባንተ ላይ ተፅኖ የሚያደርጉትን ሀሳቦች ንቁ ወደ ሆነዉ ክፍል እስካላመጣህ ድረስ እነሱም አንተን መምራታቸው አንተም እጣፈንታዬ ነው እያልክ መኖርህ ይቀጥላል”
3. ”መልካም ነገሮችን ይዘዋል እና በህይወትህ ከባድ እና የሚገዳደሩ ነገሮችን አመስግን በእዉነታዉ ለጤናማ እድገት፣ ራስን ለመሆን እና እውነተኛው እኛነታችን ላይ ለመድረስ ተግዳሮት አስፈላጊ ነው“
4. ”የትኛዉም የምታገኘዉ ሰው አንተ የማታቀዉ የሆነ ነገር ያውቃል ስለሆነም ሁሌም ለማወቅ ጉጉት ይኑርህ ከነሱም ተማር”
5. ”እኔ ለመሆን የመረጥኩትን እንጂ በኔ ላይ የሆነብኝ ነገር ውጤት አይደለሁም”
6. “ዓለም ስለማንነትህ በሚጠይቅህ ግዜ ማን እንደሆንክ ካላወክ በምላሹ ዓለም በራሱ ስለአንተ ይነግርሀል"
7. “አንድ ሰው ይበልጥ ባወቀ ቁጥር ብቸኛ እየሆነ ይመጣል”
8. “በሌሎች ላይ አይተነው የሚያስቆጣን ነገር ሁሉ አራሳችንን እንድንረዳ መንገድ ይመራናል”
9. ”ህይወት የእውነት የሚጀመረው ከአርባ ዓመት በኃላ ነው እስከዛ በነበረው እየኖርክ ሳይሆን ጥናት እያደረግክ ነው”
10. ”አንተነትህ የሚገለፀዉ በድርጊትህ እንጂ በምታወራው አይደለም እና አድርገው”
ፍ/ማርያም ተስፋዬ (የሥነልቦና ባለሙያ )
@melkam_enaseb
የጤና ወግ ዛሬ በቴሌግራም ቀጥታ ስርጭት የመማር እክል በሚል ርዕስ የሚደረገው ውይይት ላይ ይቀላቀሉ።
እንግዶች:
ተባባሪ ኘሮፌሰር አበባየሁ መሰለ (የፋና የተግባቦት እና የመሰረታዊ ትምህርት ድጋፍ መስጫ የበጎ አድራጎት ማህበር መስራች እና ስራ አስኪያጅ)
አቶ ያፌት ከፈለኝ (የአብርሆት ሳይኮቴራፒ ማዕከል መስራች)
የመማር እክሎች የማሰብ ችሎታ ወይም ጥረት ማነስን የሚያመለክቱ አይደሉም።
የበለጠ ለመረዳት ውይይቱን በቀጥታ ይከታተሉ!
🗓 እሁድ ሚያዚያ 13, 2016
⏰ ከምሽቱ 12 ሰዓት (በኢትዮጵያ)
ውይይቱን ለመቀላቀል እዚህ ይጫኑ ⬇️
/channel/yetenaweg?livestream
@melkam_enaseb
ምዕናባዊ ኦቲዝም፤ የዲጅታል ዘመን ልጆች ስጋት
ባለሙያዎች እንደሚሉት በተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ በታብሌት፣ በቴሌቪዝን እና በሌሎች ዲጅታል መሳሪያዎች ላይ ረዘም ያለ ጊዜ የሚያሳልፉ ልጆች ለጭንቀት እና ለመረበሽ፣ ለትኩረት ማጣት፣ ለንግግር እና ለቋንቋ መዘግየት እንዲሁም ለግንዛቤ እድገት ውሱንነት ይዳረጋሉ። የሰዎችን ስሜት የመረዳት እና የመግባባት ችሎታቸውንም ይቀንሳል።
በዚህ ዙሪያ #DW ያዘጋጀውን ፅሁፍ ያንብቡ ⬇️
https://p.dw.com/p/4erN2?maca=amh-Facebook-dw
@melkam_enaseb
ጤናማ ህይወትን መምራት እንዴት ይቻላል?
ጤናማ መሆን ማለት በአዕምሮ፣ በአካልና በስሜት ሙሉ ጤንነት ሲሰማን ማለት ነው፡፡
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል በበሽታ እንዳንጠቃ ከማገዙም በላይ ጤናችን ስንጠብቅ ለራሳችን ያለን ግምት መልካም እንደሚሆን የተለያዩ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ደስተኛ፣ የተረጋጋና ስኬታማ ህይወት እንድንኖር ይረዳናል፡፡
ምንም እንኳን የተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ሁኔታዎች ጤናማ ህይወትን ለመምራት አሉታዊ ተጽዕኖ ቢፈጥሩም አኗኗራችንን እና ልማዶቻችንን በመቀየር ጤናማ ህይወት መኖር እንደሚቻል ነው ጥናቶች የሚያመላክቱት።
ጤናማ ህይወት ለመኖር የሰው ልጅ የተለያዩ የህይወት ዘይቤዎችን ይተገብራል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ፦
• የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣
• የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣
• ክብደትን መለካትና መቆጣጠር፣
• በቂ ውሃ መጠጣት፣
• ለረዥም ጊዜ ያለመቀመጥና ኮምፒውተርና ሌሎች ስክሪን ላይ የምናጠፋውን ጊዜ መቀነስ፣
• በቂ እንቅልፍ መተኛት፣
• ከመጠን ያለፈ አልኮል ያለመውሰድ፣
• ቁጣና መሰል ስሜቶችን መቆጣጠር፣
• ጭንቀትን ማስወገድ፣
•የጤና ክትትል ማድረግና መሰል የጤናማ አኗኗር ዘይቤዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በተጨማሪም ከሰዎች ጋር ያለንን ማህበራዊ ግንኙነት በትኩረት መመልከት ያስፈልጋል። ከጓደኞች፣ ከቤተሰብና ጎረቤት እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን የዕለት ተዕለት ግንኙነት ማሻሻልና መልካም ማድረግ ለጤናማ ህይወት አስፈላጊ እንደሆነ የሜዲሲን ኔት መረጃ ያመላክታል፡፡
@melkam_enaseb
ታዳጊ ልጆች/ወጣቶች እና የአእምሮ ጤና፦
- የታዳጊ ልጆች እድሜ (ጉርምስና) ልዩና ወሳኝ ጊዜ ነው:: አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ለውጦቹም ከፍተኛ ናቸው።
- በዚህ ጊዜ ላይ ለድህነት፣ ለጥቃት (አካላዊም ፆታዊ) መጋለጥ እዚህ ዕድሜ ላይ ላሉ ልጆች ለአእምሮ ጤና መታወክ የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል::
አጋላጮች፦
▫️የአቻ ግፊት
▫️አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች
▫️አካላዊ ወይም ጾታዊ ጥቃት
▫️የቤት ውስጥ ሰላም መጓደል
▫️የማንነት ጥያቄ
▫️የሚዲያ ተጽዕኖ
▫️ከፍላጎት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች የተወሰኑት ናቸው።
- በተለይም የአዕምሮ እድገት ውስንነት፣ የተለያዩ የነርቭ ችግሮች፣ የቅርብ ቤተሰብ ድጋፍ የሌላቸው ታዳጊ ልጆች/ወጣቶች ደግሞ የበለጠ ለአዕምሮ ጤና መታወክ የተጋለጡ ናቸው።
ከስሜት ጋር የተያያዙ ችግሮች፦
* ከልክ በላይ ጭንቀት
* የስሜት መዋዠቅ
* ድባቴ፣ ራስን ማግለል አልፎም *በህይወት መቆየት አለመፈልግ
የባህሪ ችግሮች፦
° ትኩረት ማጣት፣
° ለነገሮች መቸኮል፣
° የፀባይ ለውጥ መኖር
የአመጋገብ ችግር፦
➡ ውፍረት እንዳይመጣ ከሚል ከፍተኛ የሆነ የአመጋገብ ችግር ነው።
የስነ-ልቦና ቀውስ፦
• ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ ያደርጋል።
• ራሳቸውን በተለያዩ ሱሶች ይጎዳሉ።
• ከማህበረሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድርበታል።
- ይህ እንዳይሆን ምን እናድርግ?
▪️ቤተሰብ ልጆቹ በሰውነታቸው ላይ ለውጥ እየተካሄደ እንደሆነ በመረዳት ለልጆቹ ከምን ጊዜውም በላይ ቅርብ መሆን አለበት።
▪️ራሳቸውን በተለያዩ ዓይነት ስራዎቸ(እንደ ስፖርት ያሉ ነገሮች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ)፣ የመፍትሄ ሰዎች እንዲሆኑ፣ በጤነኛ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ ሁሉም ሰው የድርሻውን ማድረግ አለበት።
#WHO #TikvahEthiopia
@melkam_enaseb
ወርሃዊው የሜንታል ሄልዝ አዲስ መርሃ ግብር ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓም በብይነ መረብ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ይደረጋል::
በዕለቱ በአእምሮ ጤና ዙሪያ የሚያጠነጥነው “የሁሉ” የልብወለድ መፅሃፍ ላይ ከዶ/ር አዜብ አሳምነው ከዶ/ር ዮናስ ላቀው እንዲሁም ከደራሲው ከዶ/ር ዳዊት አሰፋ ጋር የኦንላይን ውይይት ይደረጋል፡፡
በዕለቱ ለመታደም ይህን መስፈንጠሪያ ይጠቀሙ፡፡ ⬇️
https://meet.google.com/gsd-iztg-rop
@melkam_enaseb
Paranoid Personality Disorder|የተጠራጣሪነት የስብዕና መዛነፍ
በማህበረሰባችን ስለመጠራጠር አስፈላጊነት የሚያወሱ የተለያዩ ምሳሌያዊ ንግግሮችን መጥቀስ ይቻላል።
'ያልጠረጠረ ተመነጠረ'
'... ያመነ: ጉም የዘገነ'...
ታዲያ ጥርጣሬ ሲበዛ በራስ ጥላ የሚያስበረግግ አንዳች ክፋ የመንፈስ ደዌ ይሆንብናል።
አንዳንድ ሰዎች አሉ መጠራጠር የባህርይ ገንዘባቸው የሆነ ጥላቸውን ሳይቀር የሚጠረጥሩ እነዚህ ሰዎች፦
- ያለ በቂ ማስረጃ ሰዎችን ከመሬት ተነስተው መጠራጠር ይቀናቸዋል። ዘወትር ያለ በቂ ምክንያት ሰዎች እያሴሩባቸው እንደሆነ ያስባሉ።
- የትዳር አጋራቸውን እንዳልታመኗቸው ሁሉ ይጠረጥሯቸዋል።
- ሰዎች ማመን ዳገት የመውጣት ያህል ይከብዳቸዋል። የነዚህን ሰዎች እምነት ለማግኘት መሞከር ተራራን እንደመግፋት ነው ይላሉ የቀረቧቸው።
- ከሌሎች ጋር ከማውራት ይቆጠባሉ፤ በንግግራችን ብንጠቃስ ብለው ስለሚያስቡ።
- ሁሉንም ነገር በአይነቁራኛ እና በጥርጣሬ አይን ማየት ልማዳቸው ነው።
- ቂመኞች ናቸው፤ ነገር በቀላሉ አይረሱም።
አንዳንድ ሰዎች ላይ እነዚህ ምልክቶች ከአስራዎቹ እድሜ ጀምረው ሊታዩ እና በተለያዩ የህይወት መስኮቻቸው ላይ ጥላቸውን ሊያጠሉባቸው ይችላሉ። ይህ ከልክ ያለፈ የተጠራጣሪነት የባህርይ መዛነፍ Paranoid Personality Disorder ይሰኛል። ከ Cluster A የስብዕና መዛነፎች አንዱ ነው።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
ይቅርታ!
ይቅር ባይነት ይቅር ለሚለውም ሆነ ይቅርታ ለሚደረግለት ሰው ጠቃሚና አስፈላጊ ተግባር ነው።
የይቅርታ 6 ጥቅሞች፡-
1.ስሜታዊ ፈውስ፡- ይቅርታ የስሜት ቁስልን የመፈወስ ኃይል አለው። ይቅር ባይ ሰው ቁጣን፣ ንዴትን እና ሌሎች አሉታዊ ስሜቶችን እየተላቀቃቸው እንዲሄድ ያስችለዋል። እነዚህን አሉታዊ ስሜቶች በመልቀቅ ይቅርታ ስሜታዊ ፈውስ ያመጣል እና ወደ ውስጣዊ ሰላም እና ደህንነት ይመራዋል።
2.የጭንቀት መቀነስ፡- ቂም መያዝ የማያቋርጥ ጭንቀትና ውጥረትን ይፈጥራል። ይቅር ስንል እራሳችንን ከአሉታዊ ስሜቶች የማያቋርጥ ሸክም ነፃ እናደርጋለን፣ ይህም የጭንቀት ደረጃዎችን ይቀንሳል። ይህ ደግሞ በአካላዊ እና በአዕምሮአዊ ጤንነታችን ላይ በጎ ተጽእኖ ይኖረዋል።
3. የተሻሻለ ግንኙነት፡- ጤናማ እና አወንታዊ ግንኙነቶችን ለመጠበቅ ይቅርታ አስፈላጊ ነው። መግባባትን፣ መተሳሰብን እና ርህራሄን ያሳድጋል፣ ይህም የተበላሹ ግንኙነቶችን ለመጠገን እና ለማጠናከር ያስችለናል። ይቅር በመባባል፣ ለተሻለ ግንኙነት፣ እምነት እና ከሌሎች ጋር ለመስማማት መሰረት እንጥላለን።
4.ደስታን መጨመር፡- ቁጣንና ንዴትን መያዛችን በሕይወታችን ውስጥ ያለንን አጠቃላይ ደስታ እና እርካታ ይቀንሳል። በሌላ በኩል ይቅርታ መራራነትን እንድንተው እና የበለጠ ደስታን እና እርካታን እንድንለማመድ ያስችለናል። ይቅርታን በመምረጥ፣ ወደ ህይወታችን ለመግባት ለአዎንታዊ ስሜቶች እና ልምዶች ቦታ እንፈጥራለን።
5.ግላዊ እድገት እና ፅናት፡- ይቅርታ ለግል እድገት እና ፅናት ሀይለኛ መሳሪያ ነው። የራሳችንን ድክመቶች መጋፈጥ፣ ኢጎአችንን ትተን መተሳሰብን እና መረዳትን ማዳበርን ይጠይቃል። በይቅር ባይነት፣ ጽናትን እንገነባለን፣ ስሜታዊ አእምሮአችንን እናሳድጋለን፣ እናም ግጭቶችን እና ውድቀቶችን ለመቋቋም የበለጠ ዝግጁ እንሆናለን።
6.የተሻለ የአእምሮ እና የአካል ጤና፡- ይቅርታ ከብዙ አእምሯዊና አካላዊ የጤና ጠቀሜታዎች ጋር የተያያዘ እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል። የደም ግፊትን ይቀንሳል፣ የድብርት እና የጭንቀት መታወክ አደጋዎችን ይቀንሳል፣ እና አጠቃላይ የልብና የደም ቧንቧ ጤናን ያሻሽላል። ይቅርታ በበርካታ ደረጃዎች ላይ ደህንነትን ያበረታታል።
ማጠቃለያ፣ ይቅርታ በስሜታዊ፣ አእምሯዊ እና አካላዊ ደህንነታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የተለያዩ ጥቅሞችን ይሰጣል። ይቅርታን በመምረጥ ለፈውስ፣ ለእድገት እና ለተሻለ ግንኙነት እድል እንፈጥራለን።
(Seid Ahmed)
@melkam_enaseb
የጥገኝነት ማንነት መዛባት (Dependent Personality Disorder)
አካል ሊታመም እንደሚችለው ማንነትም ይታመማል። ሰዎች ሊኖራቸው የሚገባው ሳይኖራቸው (deficiency)፣ ወይንም ነገሮች ከልክ ሲያልፉ (excessive) አልያም በማህበረሰቡ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ነገርን ሲያንጸባርቁ (Abnormal) የማንነት መዛባት (personality Disorder) ተፈጠረ ልንል እንችላለን። የማንነት መዛባት በዋናነት የምናስብበትን፣ የሚሰማን ስሜትእን፣ የእለት ተእለት ተግባራችንን በተገቢው መንገድ እንድናፈጽም እክል የሚፈጥር ነው። በዛሬው ጽሁፍ ውስጥ ጥገኛ የመሆን የማንነት መዛባት (DPD) ምልክቶቹን፣ ምክንያቶችንና መፍትሄውን እናያለን።
ምልክቶች (Symptoms)
▸ ያለ ሰዎች እርዳታና ድጋፍ ምንም አይነት ውሳኔ መወሰን አለመቻል
▸ ያለ ሌሎች ድጋፍ ራስን ችሎ ስራ ለመስራት አለመቻል
▸ ሁሌም ከሰዎች የተለየ እንክብካቤን መጠበቅ
▸ ብቸኝነትንና መተውን በጣም መፍራት። የፍቅር ግንኙነት በተለያየ መንገድ ቢቆም እንኳን በፍጥነት ሌላ የፍቅር ግንኙነት መጀመር
▸ ተቀባይነትን ሊያሳጣኝ ይችላል በሚል ምክንያት ምንም ነገርን አለመቃወምና ያላመኑበትን ነገር ማድረግ
▸ በሌሎች ሰዎች የሚደርስባቸውን ተገቢ ያልሆነ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶችን በዝምታ ማለፍ
▸ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የግል ጥቅምን አሳልፎ መስጠት
▸ ማንኛውንም አይነት ትችት እንደ ጦር መፍራት
▸ ከፍተኛ የሆነ ብራስ መተማመን ማጣት
ምክንያት (Causes)
ስነ ህይወታዊ (biological) ምክንያት እንደሚኖረው የዘርፉ ምሁራን ይስማማሉ። ከዚህ በተጨመሪ ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ምክንያቶችም ለዚህ የማንነት እክል አስተዋጽኦ አላቸው። እነዚህም ብዙውን ጊዜ ቁጥጥር በበዛበት ቤተሰብ ውስጥ ማደግ፣ በልጅነት የሚወዱትን ሰው ማጣትና ጥቃት በበዛበት ግንኙነት ውስጥ ረጅም ጊዜ ማሳለፍ ለዚህ ምክንያት ከሚሆኑት ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው።
ህክምና (Treatment)
ብዙውን ጊዜ የጥገኝነት የማንነት እክል ያለባቸው ሰዎች አስፈላጊውን ህክምና ካላገኙ ወደ ድባቴ፣ ሱስና ከፈተኛ ለሆነ ጥቃት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። የስነ ልቦና ህክምና (psychotherapy) ህይወታቸውን በተገቢው መልኩ እንዲመሩ እንደሚያስችላቸው የስራ ልምዳችንና ጥናቶች ያሳያሉ።
የጥገኝነት ማንነት ዝንባሌ አለብኝ እንዴ የሚል ሃሳብ ከመጣብዎት 3 ደቂቃ ወስደው ከታች ያለውን ሊንክ በመጫን ራስዎን በመገምገም ስለ ራስዎ የበለጠ ማወቅ ይችላሉ። የሚወስዱት ሙከራ ግን በባለሙያ የሚደረግን ምርመራ (Diagnosis) እንደማይተካ ያስታውሱ።
https://www.idrlabs.com/3-minute-dependence/test.php
Reference: Diagnostic and Stastical Manual of Mental Disorders 5
በኤርሚያስ ኪሮስ (Counseling Psychologist)
@melkam_enaseb
ለውይይት መድረክ ተጋብዘዋል!
ድባቴ እና ሱሰኝነት በወንዶች ላይ
📅 ቀን፡ እሁድ ሰኔ 16፣ 2016
📍 ቦታ፡ አዲስ አበባ፣ ቦሌ ዮድ አቢሲኒያ አካባቢ፣ በሴፍ ላይት ኢኒሺዬቲቭ አዳራሽ
በጎግል አቅጣጫ ማሳያ ለመጠቀም፡ https://lnkd.in/efUDB3SR
ሰኔ ወር የወንዶች የአዕምሮ ጤና ግንዛቤ ማስጨበጫ እንደመሆኑ መጠን ለዚህ ውይይት መድረክ ስንጋብዝዎት በታላቅ ደስታ ነው፡፡
ይህ የውይይት መድረክ በአባቶቻችን፣ በወንድሞቻችን፣ በጓደኞቻችን፣ በሥራ ባለደረቦቻችን፣ በቤተሰቦቻችን ወይም በጎረቤቶቻችን ላይ የሚከሰተውን የድባቴ እና የሱሰኝነት ችግርን ከአዕምሮ ጤና ጋር ያለውን ግንኙነት በጥልቅ የሚዳሰስ ይሆናል፡፡
ይህንን ማስፈንጠሪያ: https://lnkd.in/eBaBWwZw በመጠቀም ፈጥነው ይመዝገቡ፡፡
በጋራ በአዕምሮ ጤና ላይ ያለውን የተሳሳተ እና መጥፎ አመለካከት እንስበር፡፡
@melkam_enaseb
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታይ እህት/ወንድሞቻችን፣ እንኳን ለኢድ አል‐አድሀ በዓል አደረሳችሁ!
መልካም በዓል!
@melkam_enaseb
መዋሸት ከአዕምሮ ጤና ችግር ጋር ምን ያገናኘዋል?
መዋሸት ከልጅነት ዕድሜ ይጀምር እና እስከ እድሜ አመሻሽ ድረስ ሊቀጥል ይችላል። ውሸት የህመም ምልክት እና የስብዕና መለያ ተደርጎ ይታሰባል፡፡
ውሸት ህመም ነው ማለት ባይቻልም ሲደጋገም ግን እንደ ህመም ባይወሰድም የህመም ምልክት ግን ሊሆን ይችላል፡፡
ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ውስጥ ሊዋሹ የሚችሉ ሲሆን፤ ጊዜ እና ቦታ እየመረጡ የሚዋሹ እና በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ መዋሸትን የሚመርጡ በማለት በሁለት መልኩ ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡
ለመዋሸት እንደ ምክንያት የሚነገሩ መላምቶች፦
• የአእምሮ ጭንቀት
• የጤና እክል
• ዝቅተኛ በራስ መተማን
• በሰዎች ዘንድ ተፈላጊነትን ለመጨመር በማሰብ
• የናርስሲሲት ስብዕና ያላቸው ሰዎች (አፍቅሮተ ራስ)
• ከዚህ በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ የሚዋሽ ሰው ካለ ህጻናት ውሸትን እየተላመዱ እንዲያድጉ ያደርጋል፡፡
በመዋሸት ሌሎችን ለመጉዳት የሚሞክሩ ሰዎች ቢኖሩም ያለፈ የህይወት ታሪካቸው በሚያሳድርባቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ብቻ ሰዎች ሊዋሹ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች ለምን እንደሚዋሹ ምክንያቱን ባይቁትም ፍላጎታቸው መዋሸት ብቻ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡
የመዋሸት ፍላጎታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ይጨምር እና በመዋሸታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ሲናገሩም ይስተዋላል፡፡ ሰዎችን ያለ ምክንያት ማታለል፣ አመለካከታቸውን ማሳት የስብዕና እክል ተደርጎ ይታሰባል፡፡
በህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ጉዳቶች ሰዎች እንዲዋሹ እንደ ምክንያት ይነሳል ፍርኃትም ለመዋሸት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆን ብሎ መዋሸት፣ ሀላፊነትን አለመውሰድ፣ እንደ ታመሙ ማስመሰል፣ ግልፍተኛ መሆን እና የሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሚዋሹ ሰዎች ይስተዋላሉ፡፡
እንዴት መዋሸትን ማቆም ይቻላል፤
በሰዎች እንዋሻለን የሚለው አመለካከት አለመኖሩ ለሚዋሹ ሰዎች በስነ ልቦና ባለሙያ የሚደረግላቸውን ህክምና አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
ሰዎች በቅድሚያ ስለ ውሸት እራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል፤ በንግግር ህክምና የመዋሸት ባህሪን ማከም ይቻላል፡፡ በህክምናው ሰዎች የሚዋሹበትን ምክንያት እንዲረዱ ማድረግ እና ሌሎች ተጓደኝ የአእምሮ ህመሞች ካሉ ማከምን ያካትታል።
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
የማህበራዊ ጭንቀት/ፍርሃት (Social Anxiety Disorder) or Social Phobia - ክፍል 1
በማኅበራዊ ፍርሃት/ጭንቀት የሚሰቃዩ ሰዎች በሕዝብ ፊት መቅረብ ይፈራሉ። የፍራቻቸው ዋና ጽንስ ደግሞ የሚዋርዱ ወይም የሚያሳፍር ድርጊት እንደሚፈጽሙ ማሰብ ነው።
ምንም እንኳን በህዝብ ፊት ቆሞ ንግግር ማድረግ በአብዛኞቻችን ዘንድ ምቾትን ቢነሳም፤ የ “ማህበራዊን ጭንቀት” ህመም ለይቶ ለማወቅ ከፍተኛ የሆነ የጭንቀት መጠን፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ ወይም ዘርፈ ብዙ በአካል፣ በስራ፣ በትምህርት ጉዳት ሲኖረው ነው።
ስርጭት
- ከ 5% እስከ 12% የሚሆኑ የአለማችን ህዝብ በዚህ ህመም የሰቃያሉ።
- ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ያለው ስርጭት ከፍተኛ ነው። ሆኖም ግን ወንዶች ከሴቶች በተሻለ ወደ ህክምና ይመጣሉ። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ወንዶች ለማህበራዊ ተሳትፎ ከሴቶች በበለጠ ጫና ስለሚበዛባቸው እንደሆነ ስለሚገመት ነው።
- ማኅበራዊ ፍርሃት በይበልጥ የሚከሰተው በጉርምስና እድሜ ለይ ሲሆን አብዛኞቹ ተጎጂ ሰዎች ከልጅነት የጀመረ የጭንቀት ታሪክ እንዳላቸው ይገመታል።
- በቤተሰባዊ ሃረግ አለው እድሉ በ 3 እጥፍ ሊጨምር ይችላል።
ምልክቶች
1. ማኅበራዊ ጭንቀት ውስን በሆኑ ሁኔታዎች ለይ ብቻ ወይም ደግሞ አጠቃላይ የማህበራዊ ግንኙነቶችን ሊገደብ ይችላል።
ውስን ሁኔታዎች ስንል “የአፈፃፀም ጭንቀት” (“Performance anxiety”) ማለት ሲሆን እንደ ምሳሌ፦ በአደባባይ መናገር፣ መጻፍ፣ ሬስቶራንት አልያም ገላጣ ቦታ መመገብ፣ የህዝብ መጸዳጃ ቤት መጠቀም፣ ወዘተ.... ያጠቃልላል።
አጠቃላይ ማህበራዊ ግንኙነቶች ስንል ደግሞ እንደ ምሳሌ፦ ከሰዎች ጋር መገናኘት፣ ወደ ትምህርት ቤት ወይም ወደ ሥራ መሄድ፣ ወደ ገበያ መሄድ፣ ወዘተ.... ይይዛል።
2. በማኅበራዊ ጭንቀት የሚቸገሩ ሰዎች በሚያሳዩት የጭንቀት ምልክት ምክንያት በሌሎች ሰዎች ዘንድ በአሉታዊ ሁኔታ የሚገመገሙ ይመስላቸዋል፤ ማለትም፦ የሚዋረዱ ወይም የሚያፍሩ አልያም ሌሎችን የሚያሳዝኑ)።
3. ማኅበራዊ ተሳትፎ ሁኔታዎች ሁልጊዜ በሚባል ደረጃ ፍርሃትን ወይም ጭንቀትን ያስከትላሉ።
- በልጆች ላይ ፍርሃቱ ወይም ጭንቀቱ የሚገለጸው በማልቀስ፣ በንዴት፣ ቁጣ፣ ማደንዘዝ፣ መሸማቀቅ ወይም በማህበራዊ ሁኔታዎች ውስጥ መናገር አለመቻል ሊገለፅ ይችላል፡፡
4. ማኅበራዊ ተሳትፎዎች ሁኔታዎች ይሸሹታል፤ ግዴታ ከሆነ ደግሞ በከፍተኛ ፍርሃት ወይም በጭንቀት ያሳልፉታል።
5. ጭንቀቱ፣ ፍርሃቱ ማህበራዊ ሁኔታው ከሚፈጠረው ትክክለኛ ስጋት ጋር ተመጣጣኝ አይደለም የተጋነነ ነው።
6. የማኅበራዊ ፍርሃት፣ ጭንቀት ወይም ሽሽት ቋሚ እና ከ6 ወር ወይም ከዚያ በላይ የሚቆይ ነው።
7. በማህበራዊ፣ በስራ፣ በትምህርት ወይም በሌሎች አስፈላጊ የህይወት ሂደቶች ለይ ከፍተኛ ጫና ወይም ጉዳት ያመጣል።
የማህበራዊ ጭንቀት ምልክቶች ከከፈተኛ ድንጋጤ (Panic disorder)፣ የስብዕና ችግር (Avoidant personality) እና ዓይናፋርነት (Shyness) ጋር ሊመሳሰሉ ይችላል።
ተያይዞም በሱስ አጠቃቀም ችግር፣ አልያም አካልዊ ህመምሞች እንደ ፓርኪንሰን በሽታ፣ አለቅጥ ውፍረት፣ እሳት አደጋ፣ ወዘተ...ጋር አለመዛመዱን መመርመር አስፈላጊ ነው።
ብዙውን ጊዜ በሽታው ሥር የሰደደ ቢሆንም ምልክቶቹ በሁኔታዎች ሲለዋወጡ ይታያል፤ ትንሽ ውጥረትም ያባብሰዋል።
በቀጣይ ስለ ማኅበራዊ ጭንቀት/ ፍርሃት ህክምና እናቀርባለን፤ እስከዛው መልካም ጊዜ።
ዶ/ር መሀመድ ንጉሴ (ሳይካትሪስት)
@melkam_enaseb
የንግግር ህክምና
የንግግር ህክምናን በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ የተሳሳተ አረዳድ መኖሩ ይነገራል፡፡ ይህም የንግግር ህክምና የምክር አገልግሎት መስጠት ነው የሚል እሳቤ ነው፡፡
የምክር አገልግሎት ለአእምሮ እክል ወይም ህመም የሚሰጥ ቢሆንም የንግግር ህክምና ነው ማለት አለመሆኑም ይገለጻል፡፡
በንግግር ህክምና የአይምሮ እክል ያጋጠመውን ታካሚ የልጅነት ጊዜ አስተዳደግን የሚመረምር እና ያጋጠመውን ችግር ከስር ከመሰረቱ የሚያጤን ሲሆን፤ ታካሚው የችግሩን መንስኤ እንዲገነዘብ የሚረዳ የህክምና መንገድ ነው፡፡
በዚህ የህክምና ሂደት ላይ ታካሚዎች የሚሰማቸውን የውስጥ ሀዘን፣ ንዴት፣ ሃሳባቸውን እና ያለፉበትን መልካም ሆነ መጥፎ አጋጣሚዎችን በነጻነት የሚናገሩ ሲሆን፤ ባለሞያው ችግሩን በትኩረት በመረዳት የትኛው ጉዳይ በህይወታቸው ላይ ተጽዕኖን ሊያሳድር እንደሚችል እና ህመሙ ሚታከምበትን ሁኔታ የሚመረምር ይሆናል፡፡
የህክምና ሂደቱ በባለሞያው እና በታካሚው መካከል የሚካሄድ በመሆኑ የታካሚው ሚስጥር እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡
የንግግር ህክምና፦ ለጭንቀት፣ ድባቴ እና መሰል አእምሮ እክሎች የንግግር ህክምናን እንደ መጀመሪያ የህክምና ሂደት የሚሰጥ ነው። እንዲሁም ድንገተኛ ሃዘን ሲያጋጥም፣ ከአደጋ በኋላ የሚከሰት የአይምሮ እክልን፣ በትዳር ህይወት የሚያጋጥሙ ግጭቶችን፣ ለሱስ ለተጋለጡ ሰዎች፣ አረዳድ እና ባህሪን ለማረቅ፣ ጠባሳ ሆነው የቀጠሉትን በልጅነት ጊዜ የተከሰቱ መጥፎ የህይወት አጋጣሚዎችን ለማከም የሚሰጥ ነው።
በልጅትነት ጊዜያት ላይ የሚያልፉ ጥሩም ሆኑ መጥፎ የህይወት ክስተቶች ለሰዎች የወደፊት ህይወት እና ስነልቦና ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራሉ፡፡
በመሆኑም ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ልጆቻቸው የሚናገሩት ንግግር የተገራ፣ የሚተገብሯቸው ድርጊትች የተቆጠቡ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የብዙዎች የአእምሮ እክሎች በልጅነት ጊዚያት ላይ በሚፈጠሩ መጥፎ ጠባሳዎችን ተከትሎ የሚከሰቱ ናቸው።
የሰዎች አሉታዊ ንግግር በሌሎች ላይ ለበታችነት ስሜት፣ ምንም ማድረግ አልችልም ብሎ ለማሰብ እና አንዳንዴም ከልክ በላይ ለራስ ክብርን መስጠት ሊያጋልጥ በመቻሉ፤ አንደበት ሊታረም እና ለሰዎች አይምሮ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
የንግግር ህክምና ውጤታማ ነው። በማህበረሰቡ ዘንድ የተለመደው የተሳሳተ አረዳደድ ሊታረም ይገባል እና ሰዎች የሚያስጨንቃቸውን እና የሚያጋጥማቸውን መጥፎ የህይወት ክስተቶችን ከባለሞያ ጋር በመነጋገር የአእምሮ ጤናቸውን መጠበቅ ይችላሉ፡፡
ህክምናው በዋናነት በልጅነት የእድሜ ክልል ያጋጠሙ ሁኔታዎችን የሚያስታውስ፣ የትኛው የህይወት ገጠመኝ የሰዎችን ስነልቦና እና የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ጫና የሚያሳድሩ መንስዔዎችን የሚመረምር በመሆኑ በወላጅ አልያም በአሳዳጊዎች ዘንድ ከታች የተዘረዘሩት ቢለመዱ ጥሩ ነው።
በተቻለ መጠን ቁጡ አለመሆን፣ የልጆች ባህሪ ላይ መስራት፣ ከቁስ በተጨማሪ ፍቅርን ለልጆች መስጠት እና ልጆች የሚተማመኑበት ወላጅ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው (የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት)
@melkam_enaseb
ጥናት!
ተመራማሪዎች በቀን ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ የእግር ጉዞ ማድረግ የአዕምሯችንን አቅም ለማሳገድ እንደሚረዳ አስታወቁ።
አዲስ የተሰራ የኒውሮሳይንስ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ለ20 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ የአዕምሯችን አዲስ መረጃ ለመውሰድና ለመያዝ እንዲዘጋጅ ያደርገዋል።
በተለይም ውሳኔ ለመስጠት፣ ጭንቀትን ለመቆጣጠርና፣ በባህሪያችን ዙሪያ የሚያቅደው የአእምሯችን ክፍል ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ እንዳለው ነው ተመራማሪዎች ያስታወቁት።
ሌሎች አይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች የአዕምሮ ጤናን ለመጠበቅ እንደሚረዱ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ይህኛው ጥናት ግን የግር ጉዞ እና የአእምሮ አቅም ላይ ትኩረትን ያድረገ እንደሆነም አስታውቀዋል።
በዚህም በቀን ለ20 ደቂቃ እና ከዚያ በላይ የእግር ጉዞ ማድረግ የአእምሮን አቅም እንደሚያሳድግ እና ምንም እንቅስቃሴ ካለማድረግ የተወሰነ የእግር ጉዞ ማድረግ እንደሚሻልም ጥናቱ አመላክቷል።
የሳንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጥናቱን ባከናወኑበት ወቅት ተሳታፊዎች የእግር ጉዞ የሚያደርጉ እና የማያደርጉትን በመለየት ክትትል ያደረጉ ሲሆን፤ በዚህም ለ20 ደቂቃ የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች ተቀምጠው ከሚውሉት የተሻለ ሆነው ተገኝተዋል።
ተመራማሪዎች የአእምሮ እንቅስቃሴን በኤሌክትሮኤንሴፋሎግራፊ (ኢኢጂ) መለካት ምን እየተፈጠረ እንዳለ የተመለከቱ ሲሆን፤ በዚህም የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች ላይ ተጨባጭ እና አወንታዊ ተፅእኖዎችን አይተዋል።
Via: Alain
@melkam_enaseb
ሳይጀመር የተደመደመ ሕይወት!
Fatalistic Attitude
የሚኖሩት ኑሮ አንዴ የተወሰነና ሊለወጥ የማይችል እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ፈረንጆቹ ይህንን አመለካከት fatalistic attitude ይሉታል፡፡ ያለቀለትና ቅድመ-ድምዳሜ ተወስኖለት የተጀመረ ሕይወት እንዳለን ማመንን የሚጠቁም ሃሳብ ነው፡፡
ይህ አይነቱ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በሕይወታቸው ያለውን ምንም ነገር ለመቀየር አቅሙ እንደሌላቸው ነው የሚያስቡት፡፡ የወቅቱ ኑሯቸው ሁኔታ ለእነሱ የተመደበና ምንም ቢታገሉ ሊለወጥ እንደማይችል ያስባሉ። ስለዚህም የነበረውንና ያለውን በመቀበል ያዘግማሉ፡፡
እንደዚህ አይነት ሰዎች በዙሪያቸው ብዙ ሰዎች በማለም፣ በመስራትና በማመን ሕይወታቸውን ሲለውጡ እያዩ እንኳን ንቅንቅ አይሉም፡፡ ምክንያቱም እነዚያኞቹ በሕይወታቸው የሚያዩት ለውጥም ሳይቀር ቀድሞውኑ ለእነሱ የተወሰነላቸው እንደሆነ ስለሚስቡ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ራስን ለማሻሻል ምንም አይነት መነሳሳት ስለማይኖራቸው የመጣላቸውን እየተቀበሉና ያንኑ እየኖሩ ዘመናቸውን ይጨርሳሉ፡፡
ሕይወት ግን እንደዚያ አይደለችም፡፡ ሕይወት የምርጫ መስክ ነች፡፡ ሕይወት የዘራነውን የምናበቅልባት መሬት ነች፡፡ ሕይወት ፈቃዳችንን፣ ጉልበታችንንና ሌሎችንም እሴቶቻችንን አስተባብረን ከአንድ ደረጃ ወደሌላኛው ደረጃ እንደመሰላል የምንወጣት የምታጓጓ መስክ ናት እንጂ ታሪካቸው ተጽፎና አልቆ ያከተመለትና ፍጻሜ የተበየነባቸው ሰዎች መተራመሻ አይደለችም።
(ዶ/ር እዮብ ማሞ)
@melkam_enaseb
እኛ እራሳችንን እና ሌሎች እኛን ምን ያህል ያውቁናል?
አንዳንድ ግዜ ሰዎች እኔ እራሴን በደንብ አውቀዋለሁ ወይም እከሌን በደንብ አውቀዋለሁ ሲሉ ይደመጣል ነገር ግን የስነ-ባህሪ አጥኚዎች ሰው ራሱንም እንዲሁም ሌሎችን ሙሉ በሙሉ እንደማያውቅ እንደሚከተለው ያስረዱናል።
4ቱ ማንነቶቻችን፦
1. Open- ግልፅ ሆኖ የሚታየው የማንነት ክፍል ሲሆን እኛ ራሳችን እና ሌሎች እኛን የሚያውቁት ግልፅ የሆነው ማንነት ክፍል ነው።
2. Hidden- ድብቅ የሆነው የማንነት ክፍል ሲሆን እኛ ራሳችን የምናውቅው ሌሎች ግን ስለእኛ የማያውቁት ክፍል ነው።
3. Blind- ሰዎች ስለኛ የሚያውቁት እኛ ግን ስለራሳችን የማናውቀው የማንነት ክፍል ነው።
4. Unknown- ሌሎች ሰዎችም ሆኑ እኛ ራሳችን ስለራሳችን የማናውቀው የማንነት ክፍል ነው።
ስለዚህ ከሰዎች ጋር መልካም እና ሚዛናዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረን ከላይ የተዘረዘሩትን የማንነት ክፍሎች ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው።
ካልሆነ ግን እከሌን አውቀዋለሁ ብለው ሲያስቡ አንድ ቀን ድብቁ/ የማያውቁት ማንነት ሲገለጥ ሊጎዱ ይችላሉ። እንዲሁም ራስዎትን ራሴን በደንብ አውቀዋለሁ በማለት ሌሎች ከሚሰጥዎት ምክር ባለመማር ራስዎትን ከማሳደግ እና ከማሻሻል እንዳይገደቡ ጥንንቃቄ ያድርጉ።
በ መአዛ መንክር (ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት)
@melkam_enaseb
እራስን ካለፉ መጥፎ ክስተቶች እስር ነፃ ማውጣት!
ህይወትህ ውስጥ በተፈጠረ አንድ አሉታዊ ክስተት ምክንያት፣ በአዕምሮህ አሁንም እየተመላለሰ የሚያስቸግርህ ሃሳብ አለ? ይህ ሃሳብ ስሜቱ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ እንዴት አድርጌ ልርሳው ወይም ከትውስታዬ ልፋቀው ብለህ ታውቃለህ?
አዕምሮህን እንደትልቅ ላይብረሪ ተረዳው። ከልጅነት እስከ እውቀት አንተ ጋር የተከናወኑ ነገሮች ሁሉ በትውስታ መልክ በውስጡ እንደመጽሃፍት ተሰድረውበት ይገኛሉ። ከእነዚህ ትውስታዎች አንዳንዶቹ መልካም (አውንታዊ) ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ መልካም ያልሆኑ (አሉታዊ) ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ትውስታዎች ቢያልፉም እንደተገነዘብናቸው መጠን ዛሬም ድረስ ውስጣችን አውንታዊ ወይም አሉታዊ ስሜት ይፈጥራሉ።
በተለይ የአሉታዊ ክስተቶች ተፅዕኖ አሉታዊ ስሜት ውስጣችን በመፍጠር ብቻ የሚቆም አይደለም። ብዙ ግዜ በምንወስናቸው ውሳኔዎች ውስጥ ዛሬም ጣልቃ እየገቡ ትክክለኛ ውሳኔ እንዳንወስን ሊከለክሉንም ይችላሉ። ከዚያም ሲያልፍ ጉዳዩ በተፈጠረበት ወቅት ከደረስንባቸው መረዳቶችና ድምዳሜዎች የተነሳ፣ ወደፊት መፍጠር ከምንፈልገው ህይወት አንጻር የማይጠቅም እይታ (አመለካከት) እንድናዳብርም ያደርጋሉ።
የሚገርመው ብዙ ግዜ አሉታዊ ስሜት የሚፈጥሩትን ትውስታዎች በቀላሉ ማስታወስ፣ እንዲያውም እነዚህ ትውስታዎች ውስጥ ለረጅም ግዜ በመቆየት ራሳችንን ቶርቸር ማድረግ ለብዙዎቻችን ቀላል ነው። ምናልባት እነዚህ የምናስታውሳቸው ክስተቶች ያለፉና የማይደገሙ እንደሆኑ ብናውቅም አዕምሯችን ግን ክስተቶቹ አሁን በዚህ ቅጽበት እየተከናወኑ ያሉ እስከሚመስል ድረስ በጠንካራ አሉታዊ ስሜት ውስጥ እንድንዘፈቅ ያደርገናል። ታዲያ እነዚህ ያለፉ፣ የማይደገሙ ክስተቶች አሁን እየፈጠሩብን ካለው አሉታዊ ስሜት፣ የውሳኔ ውስንነትና፣ ጎታች አመለካከት ተፅዕኖዎች ራሳችንን እንዴት ማላቀቅ እንችላለን?
ይህን ጥያቄ ስናነሳ ብዙዎች “እርሳው ባክህ”፣ ወይም “ለበጎ ነው” ወዘተ የሚል ምላሽ ይሰጡናል። ነገርግን “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” ነውና እኛ ነገሩን ማስታወስ ፈልገን ሳይሆን አዕምሯችን ከኛ እውቅና ውጪ እያሳሰበን እንደሆነ ማን ይንገርልን?
እነዚህ በውስጣችን ተሰድረው ማለፋቸው ሳያንስ አሁንም ህይወታችንን ካመሰቃቀሉ ትውስታዎችን ለመፋታት የሚከተሉትን ማድረግ እንችላለን፦
1. እነዚህን ክስተቶች ከንደገና በማስታወስ ልንማርባቸው የምንችላቸው ነገሮች ካሉ ወረቀት ላይ በጽሁፍ ማስፈር።
2. እነዚህን ክስተቶች ከንደገና በማስታወስ ጉዳቱን የፈጠሩ ሰዎች ካሉ፣ በወቅቱ የነበረባቸውን የባህርይ፣ ስሜት እና የውሳኔ ውስንነት እንደገና አሁን ባለን መረዳት መመልከት። እነዚህ ውስንነቶች ባይኖሩባቸው ምን ሊያደርጉ ይችሉ እንደነበር ማሰብ፤ እነሱ የነበሩባቸውን ውስንነቶች እኛም ሳናውቅ እያንጸባረቅን እንዳልሆነ ማረጋገጥ።
3. የሚፈጥሩብን ስሜት ከባድ ከሆነና ከላይ ባደረግናቸው ልምምዶች ስሜቶቹንና ግንዛቤያችንን መለወጥ ካቃተን የባለሙያ ርዳታ እንፈልግ።
ዳንኤል አያሌው (Certified NLP Practitioner)
@melkam_enaseb
ወርሃዊው የሜንታል ሄልዝ አዲስ መርሃ ግብር ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓም አትላስ አካባቢ በሚገኘው በአዶር አዲስ ሆቴል ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ይደረጋል::
የዚህ ወር ርዕስም፡- “እንደ ህብረተሰብ የስነልቦና ቁስልን መገንዘብ” የሚል ሲሆን የዚህ ወር እንግዳችን የአሃ ሳይኮሎጂካል አገልግሎት መስራች እና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሞገስ ገ/ማሪያም ናቸው፡፡
ለመታደም ይህን መስፈንጠሪያ ይጫኑና ይመዝገቡ፡፡ ⬇️
https://forms.gle/Y8iPkGRELLR2cFW86
@melkam_enaseb
የውድድር ስነ-ልቦና!
የውድድር ስነ ልቦና እንደዘርፉ ባለሙያዎች ትንታኔ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡
ውድድር ሰዎች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ለማነሳሳት እንደሚረዳና አውጥተውም እንዲያሳዩበት እድል የሚፈጥር መሆኑ ይነገራል፡፡
ሆኖም የውድድር መንፈስ እንደጥቅሙ ሁሉ በትክክል መያዝ ካልተቻለ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ውድድርም የተለያዩ የጤና እክሎችን እንደሚያስከትልም ነው የሚነገረው፡፡
የውድድር ስነ-ልቦና ሰዎች በህይወታቸው ያልተመለከቱትን አቅጣጫ የሚመለከቱበት ነው። በተጨማሪም በተለያዩ መንገዶች የተሻለ ለመሆን እገዛ የሚያደርግ ነው።
ውድድር አሸናፊና ተሸናፊዎች ያሉበትና ሽንፈትን ፈጽሞ አለመቀበል ራስን አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ሲከት ይታያል፡፡ ከቤተሰብ ወይም ከጓደኛ አልያም በስራ አካባቢ የበዛ የውድድር መንፈስ ሲታይ ተመልክተው ይሆናል፡፡
ይህ የውድድርና የአሸናፊነት ጥማት የሌሎችን ስኬት ዕውቅና ከመንፈግ ጀምሮ የራስን ማንነት አለመቀበል ሊያስከትል እንደሚችልም ይገለጻል፡፡
ይህም ሰዎችን መዋሸት፣ ጫናዎች፣ ጭንቀት፣ የበታችነት ስሜት መሰማትና በቂ ነገር የለኝም በማለት ያሉበትን ቦታ አለመውደድ እና የማንነት ቀውስ ውስጥ ያስገባል።
ያለአግባብ የውድድር መንፈስ በራስ መተማመን የሚያመጣው ስሜት ነው፥ የራሴ ነገር በቂ አይደለም በሚል ሃሳብ ሌሎችን ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡ ይህ ስሜት እየቆየ ሲሄድም ቁጣ፣ ንዴት፣ ቅናት እና መሰል ስሜቶች መገለጥ ይጀምራሉ፡፡
ይህ ስሜት ከየት እንደመነጨ ማስተዋል፣ የሰዎችን ስኬት መቀበል፣ የውድድሩ ፍላጎት ራስን ከማሳደግ የመነጨ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው የሚለውን መለየት ችግሩን በወቅቱ ለመፍታት እንደሚያግዝም ይነገራል፡፡
ባርኮት ጌቱ (የስነ-ልቦና አማካሪ)
@melkam_enaseb