"ያመነ የተጠመቀ 'ቆንጆ' ይሆናል?!"
(አሌክስ አብርሃም)
ዛሬ የአንጋፋዋ ዘማሪት ሊሊ /ቃልኪዳን ጥላሁን/ ልደት መሆኑን እዛና እዚህ ከፎቶዎቿ ጋር በተለጠፉ የመልካም ምኞት መግለጫዎች አየሁ! ቆየት ካሉት የፕሮቴስታንት ዘማሪዎች የዳንኤል አምደሚካኤል እና የሊሊ መዝሙሮች ደስ ይሉኛል! ሁለቱም እንደዘመኑ በርካታ ዘማሪያን እና ሚናቸው ያለየ አገልጋዮች እውቅና አንገዳግዷቸው እዚህና እዛ እየረገጡ ሀዲዳቸውን አልሳቱም! በቅድሚያ ሁለቱም ልደታቸው የተቀራረበ ነበርና እንኳን መጀመሪያም እንደገናም ተወለዳችሁ እላለሁ🙏
የዚህ ፅሁፍ መነሻ በርካታ ሰዎች በሊሊ ልደት ታከው "ኢየሱስን ያመሰገኑበት" እና "መንፈሳዊ ስጦታ" ሊያደርጉት የሞከሩበት መንገድ የፈጠረብኝ ግርምት ነው! " እንጅ (((የሊሊ ውበትም ይሁን አለባበስ አይደለም!))) ፎቶዎቹን የተጠቀምኩት ከጠቀስኳቸው አባባሎች ጋር ተለጥፈው ስላገኘኋቸው ብቻ ነው!
((ሊሊ በ52 ዓመቷ የ25 ዓመት ወጣት የመምሰሏ እና የመቆንጀቷ ሚስጥር ጌታ ጋር መጣበቋ ነው )) የሚል ለክርስትና የቁንጅና ሳሎን ማስታወቂያ ዓይነት ግብር የሚያላብስ የመልካም ምኞት መግለጫ ተደጋግሞ ሲሰነዘር አየሁ! በዚህኛው ዙር ተናጋሪው ጨመረ እንጅ ይህ አባባል አምናም ሀቻምናም ሲባል እንዲሁ ገርሞኝ የተውክት ነበር! ደስታችሁን ለማደፍረስ ምኞት የለኝም! ማንም ሰው ቢያምርበት እሰየው! ቢመቸውም ደስታየ ነው! ግን ከቀን ወደቀን በተለይም "መንፈሳዊ" በሚባለው አኗኗር ውስጥ እየተባባሰ የመጣው "አምልኮተ ውበት" በየቤተ እምነቱ እየገዘፈ እውነትን ሲያኮስስ እያየሁ በመገረሜ ነው! አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ጎንም አለው። አካላዊ ውበትን "መንፈሳዊ ስኬት" አድርጎ ማቅረቡ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ጦስ ውስጥ እየከተተን ነው!
በዚህ ፅሁፌ "ጌታ ጋር መጣበቅ" ለአካላዊ ውበት ዋስትና እንደማይሆን ስነግራችሁ ተስፋ ላደረጋችሁ በማዘን ነው! " በስተርጅና ያበረታቸው፣ የለመለሙ " ሰዎች ታሪክ በመፅሐፉ ቢጠቀስም ጉዳዩ ብርታት ጋር እንጅ ቁንጅና ጋር አይገናኝም! ከመጣፍም ከሊቅ አፍም እማኝ እንጥራ ከተባለ ብዙ ማምጣት ይቻላል! ግን እስቲ በዙሪያችን እንጀምር ...ሊሊ በ52 ዓመቷ ወጣት የመምሰሏ ሚስጥር ጌታ ጋር መጣበቋ ነው ? እሽ ...ሩቅ አትሂዱ የምታመልኩበት አዳራሽ ውስጥ አይናችሁን ከመድረክና ፊት ወንበር ከሚደረደሩት ቆነጃጅትና ጎበዛዝት አንሱና ፣ የኋላ ወንበሮች አካባቢ ተመልከቱ ...በሰው ቤት እንጀራ በመጋገርና ልብስ በማጠብ በ25 እና ሰላሳ ዓመታቸው እንደስልሳ አመት አዛውንት የተጎሳቆሉ ጌታን የሚወዱ ፣ ውበታቸው ቅሪት ትቶ የጠፋ ወገኖቻችሁን ታያላችሁ! ጌታ ፈርዶባቸው ይሆን ከእድሚያቸው በላይ አርጅተው የታዩት?
ወደገጠር "ቸርቾች" ወጣ በሉ፣ በከባድ ጉልበት ስራ የቆረፈደ ፊት ፣እጃቸው ከመሻከሩ ብዛት ጭብጨባቸው እንደጣውላ እየጮኸ የኪቦርድ ድምፅ የሚውጥ ፣ከዕድሚያቸው እጥፍ ያረጁ ጎስቋላ ወገኖች አዳራሽ ሞልተው በፍቅር ሲያመልኩ ታገኛላችሁ ! የውበት አምላክ ፊቱን አዙሮባቸው ነው? ወደውጩ አለም ሂዱ፤ በከባድ የጉልበት ስራ ተቀጥቅጠው ፣በእንቅለፍ እጦት የናወዙ፣ ቆዳቸው ያኮፈኮፈ ሚስኪን ስደተኛ ወገኖች አምላካቸውን እንደገደል ጫፍ ገመድ የሙጥኝ ብለው ታገኛላችሁ! እርግማን ይሆን ? እኒህ ሁሉ የሚበዛ እድሚያቸውን በቤቱ የኖሩ ግን በኑሮ ድካም በአካል የተጎሳቆሉ ጌታ ጋር መጣበቃቸው ከአካላዊ ጉስቁልና ያላዳናቸው ስለምንድነው? እምነት ጎድሏቸው?
በተቃራኒው በአገር ቤት ከተሞችና በውጭ የሚኖሩ "አገልጋዮች" በነፍስ ወከፍ የታደለ እስኪመስል የተጋነነ አለባበስ ፣ ጌጣጌጥና ውበት የሚነግረን መንፈሳዊ ብርታታቸው ያሸለማቸውን ውበት ሳይሆን የኑሮ ምቾትን ፣ ውበትን ለመጠበቅ የተሰዋን ጊዜና ገንዘብ፣ ምናልባትም ለእነሱ አምሮ መታየት ከኋላቸው ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ጎስቋሎች መኖራቸውን ነው! ምቹና ወዛም ኑሮ ሁሉ ከጌታ ነው የሚሉ ቢኖሩም፣ ጌታን ክደው የወዛ ቆዳ፣ የሚያንፀባርቅ ውበት ባለቤት የሆኑ ቢሊየኖች ናቸውና ምክንያቱ ወንዝ አይሻገርም! ጉስቁልና የመንፈሳዊነትን መገለጫ እንዳልሆነው ሁሉ አካላዊ ውበትም የክርስትና መገለጫ አይደለም! የክርስትና አንኳሩ ፣ባለቤቱ ኢየሱስ ራሱ በምድር ስለነበረው አካላዊ ውበቱ በነብያት አፍ ቀድሞ ሲገለፅ "...ባየነውም ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም..." የተባለለት ጎስቋላ ነበር ብሎናል ቃሉ!ምናልባት "ጌታ ጉስቁልናየን ስለተሸከመልኝ እኔ እዘንጣለሁ" ከተባለ ...መቸስ እየለየ አልተሸከመ ስለሁሉ ስላመኑት መሰለኝ ሸክሙ (ውበትን ከጨመረ) ወይስ እንደፀጋ ላንዱ ልጁ መዘነጥ ለሌላው መጎስቆል ይሰጥ ይሆን? ዋናው ነጥብ አካላዊ ዝነጣው የሚፈጥረው ውበት መንፈሳዊ ምንዳ ሳይሆን የሰዋዊ ምቾትና ጥረት ውጤት ነው !
የሆነ ሁኖ ውበት በራሱ ችግር አይደለም ፣በዉበት እውነትን መጋረድ ግን ችግር ብቻ ሳይሆን መሀበረሰቡን የሚያነቅዝ ተላላፊ በሽታ ነው! በዚህ በሽታ ድፍን አለም ከመያዙ የተነሳ የውበት ውድድሩ ሰዎች ማንነታቸውን በቁማቸው እስከመሸጥ የሚያደረስ ዘመናዊ ባርነት ውስጥ ዘፍቋቸዋል! ይሄ ባርነት "የሰለብሪቲ መንፈስ" ሆኖ ቤተ እምነቶችን ካጥለቀለቀ ሰነበተ! በተለይ መድረክ አካባቢ ያሉ ሰዎች ራሳቸውም መቋቋም እስኪያቅታቸው የልብስ ፣የሜካፕ ፣የአቋም፣ የፀጉር ፣ የአነጋገርና አረማመድ፣ የስልክ ፣ የቤት ፣ የመኪና የሚስት እና የባለሰ እንዲሁም አኗኗር ስታይል ውድድር ውስጥ ወድቀው እያየን ነው! ለዚህ ችግር ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተው ደግሞ የተወራው የተተነፈሰውን አየር ላይ ለመዝራት በየቤተ አምልኮው የተደቀነው ካሜራ ጭምር ነው! ብዙዎቹ ካሜራማኖች ከመንፈሳዊ ውሎ በላይ የግለሰቦችን ውበትና ገመና አነፍናፊ ናቸው!
በዓለም ያሉ "ሰለብሪቲዎች" ለውበት የሚሞቱበት ምክንያት የተሰቀለላቸው ፣ የተሰዋላቸው ፣እዚህ ለመድረስ ያበቃቸው ፣ ሰው ያደረጋቸው "ውበታቸው" እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው! ውበታቸው ቢጓደል የከበባቸው ሁሉ እንደሰባራ ቅል ይወረውራቸዋል! ከፋሽኑ ዓለም እንደጥራጊ አፋፍሰው ይበትኗቸዋል! ስለዚህ ለውበታቸው የትኛውንም መስዋዕት ያቀርባሉ!ነፍሳቸውንም ቢሆን! ልብስ ሜካፕ እውቅና የህመማቸው መሸፈኛ የመኖራቸው ዋስትና ነው! ሌላ ተስፋ የላቸውም! ከዛ ውጭ ባዶ ናቸው! ዓለም ሰውነታቸውን ያመልካል፣ ውበታቸውን ነጋ ጠባ ይሳለማል ...በስማቸው ቤተ እምነት የተከፈተላቸውም አሉ! (ቢዮንሴ ምስክር ናት) አንዳንዶቹም ለውበታቸው በየሰከንዱ ከመጨነቅ በሚመጣ የአእምሮ ህመም ፣ በሰርጀሪና መደሀኒት ብዛት ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል! ጦሳቸው ከእነሱ አልፎ ለአለም ህዝብ ተርፏል! የተጋነነ የውበት ጭንቀትና ቅራቅንቧቸውን በየዘመኑ ወደተራው ህዝብ ይደፉታል! "መንፈሳዊያን ውበት አሳዳጆችን " ጨምሮ የብዙሀኑ የፋሽንና የመዋብ ልክፍት ከነዚህ ተመላኪዎች የወረደ ሳልቫጅ አስተሳሰብ ነው! ልብስና ጫማው አዲስ ይምሰላችሁ እንጅ አስተሳሰቡ ሳልቫጅ ነው!
ምን ላይ ነበር ያቆምኩት?
“ቀጥሎአል አካሄዱን ግን ቀይሯል” ብዬ ነበር። ቤተ ክርስቲያን በአካሉ ብልት ተመስላለች። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ የጸጋ ሥጦታዎች ልዩ ልዩ መሆናቸውን ለመናገር ያመጣው ምሳሌያዊ አገላለጽ ነው። የአካሉ ራስ ክርስቶስ ነው። እንግዲህ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ በመሆናቸው ለምዕመናን መንፈስ እንደፈቀደ ተሰጥተው የነበሩ ሥጦታዎች (ብልቶች) አሁን በምንም ምክንያት አላስፈላጊ የሚሆኑበት ሁኔታ አይኖርም በማለት ካሁን ቀደም ያልኩትን አጠናክራለሁ። በጠዋትዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትንቢታዊም ሆነ ተዓምራዊ የኃይል ሥጦታዎች ከነበሩ ዛሬም የማይኖሩበት ምክንያት አለመኖሩን ቤተ ክርስቲያን ከምሥረታዋ ጀምሮ እስከ ንጥቀቷ አንዲት መሆኗን አስምሬ እናገራለሁ።
ሆኖም ግን ከብሉይ ኪዳን ተሻግሮ እንደመጣ የሚታወቀው የነቢይነት አገልግሎት በአዲስ ኪዳን የሚኖረው ገጽታ ከብሊይ ኪዳኑ ጋር የሚመሳሰልበት አካሄድ አይኖረውም ብያለሁ። ለዚህም ምክንያት ናቸው ብዬ ያመንኳቸውን ከቃሉ በማጣቀስ ለማብራራት ሞክሬያለሁ። ይህ ለበ ወለድ ወይም ፈጠራ ሳይሆን ቃሉ የሚናገረን እውነት መሆኑን አንስቻለሁ። በዚሁ መሠረት ከክርስቶስ መምጣትና ከኪዳኑ መታደስ ጋር ተያይዞ ለአማኞች ከተሰጣቸው ገጸ በረከት የተነሳ የብሉይ ኪዳን ዓይነት ነቢያት አይኖሩም የሚል ሙግት ነበር የጀመርኩት። በክርስቶስ ተሰውሮ በአብ ቀኝ መቀመጡ የተነገረለት አማኝ፣ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ምሪቱን ኃይሉን ምክሩን የሚለማመድ አማኝ፣ የሕይወት መመሪያ ማኗል የሆነውን ቃሉን በእጁ የያዘ አማኝ፣ ለንጉሡም ካሕን መሆኑ የተነገረለት የአዲስ ኪዳን አማኝ የብሉይ ኪዳኑ ዓይነት ነቢይ አያሻውም የሚል ሙግት አቅርቤያለሁ።
የተቀየረው አካኼድ ምን ይመስላል? ለዛሬ ሁለት የተቀራረቡ ነጥቦችን ላንሳ:-
1. በአዲስ ኪዳን የትንቢት ሥጦታ የነቢይነት ቢሮ ሳይሆን የአገልግሎት ዕድል ነው። ግለሰብ ተኮርም አይደለም። በተለምዶ “በነቢይነት ቅባት ተቀብቻለሁ።”፣… “የነቢይነት ራእይ ተቀብያለሁ።”፣… “የነቢይነት ጥሪ ደርሶናል።”… “ለነቢይነት አገልግሎት ተለይቻለሁ”… የሚባል ልምምድ በአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማናስተውለው አንዳንዱም ፈጥረን ሌላም ከአሮጌው ኪዳን ተውሰን የምናወራው ነው። ነቢይነት ቢሮ ወይም ሹመት ሳይሆን የ አገልግሎት ድርሻ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ሲያብራራ ምን አለ? “ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ።” (1ቆሮ. 14:31) ይላል። ትምህርትና ምክር የሚገኝበት በመሆኑ የመተንበይን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ሰው ጉባኤው ላይ ከተገኘ በዚያ ጸጋ ያገልግል። ሁሉም መናገር ይችላሉ። ግርግር እንዳይፈጠርና መደማመጥ እንዲኖር ሲባል ግን አገልግሎቱ ሥርዓት በያዘ መልኩ እንዲከወን አንዱ ሲናገር ሌሎቹ መመርመር ስለሚኖርባቸው ተራ በተራ ይሁን አለ። “ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤” (1ቆሮ. 14:29) ይላል። ከጉባኤው እየተነሱ በወረፋ የሚሰጡት አገልግሎት መሆኑ ነው። ሰማይ ጠቀስ አይደለም። እኩል የአገልግሎት ጸጋ ነው።
ነቢይነትን ስናስብ እግዚአብሔር በአፉ ቃል የሚያኖርለት… ብቻውን ገዝፎ የወጣ ንቀልና ትከል የተባለ… ስለ ድላችንም ስለ ሽንፈታችን “ምን ትላለህ” እያልን ሄደን የምንጠይቀው… ነገሥታትን የሚቀባልን … “ይህ ሰው የት ይገኛል?” እየተባለ ተፈልጎ “ከዚያ ተራራ ማዶ አለ” ተብሎ የሚመጣ ዘይት በቀንድ የያዘ… በየፈፋው የሚኖር ዓይነት ሰው ነው ወደ አእምሮአችን የሚመጣው አይደል? አለዚያም ደግሞ ትራንስፖርት ተከፍሎት “አንድ የተቀባ ሰው ካንተ ጋር ይዘህ ና” ተብሎ የሚመጣ… ከጸሐይ በታች የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን ሁሉ ሂድና ና ማለት የሚችል የሚመስለው ተራራን የሚያናጋ ሰው ነው ቶሎ ልባችን የሚያስበው። አሁን አሁን ደግሞ ባለ ራዕይና መሥራች የግል ቤተ ክርስቲያን መክፈት የቻለ ፋይናንሱን ለምስቱ፣ አስተዳደሩን ለእህቱ፣ ጥበቃውን ለአጎቱ ልጅ፣ ዝማሬውን ለወንድሙ ከፋፍሎ ከበራሪ አባሎች የምትገኘውን ገንዘብ ራቫ ፎር ገዝቶባት የሚንደላቀቀው ሰው ነው ትዝ የሚለን።
ግን የአዲሱ ኪዳን ነቢያት ጉባኤ ውስጥ ናቸው። አገልጋዮች ናቸው። መንፈስ በውስጣቸው የሚያመጣውን የጊዜውን መልእክት በመሪዎች ሥርዓት አስያዥነት ተራ ሲደርሳቸው ያቀርቡና ቁጭ ይላሉ። ከዚህ ውጪ ግን “ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤ ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ።” (1ቆሮ. 14:1) ብሏል። እንጣጥ እንጣጥ የሚል ያለሥርዓት መኼድ የሚፈልግ “ቁጭ በል” ሲባል አልልም የሚል “ተራ ያዝ” ሲባል “ታየኝ”ና “ተሰማኝ” በሚል የሚንፈራፈር ካለ ዕውቅና እንዳይሰጠው ሐዋርያው ጳውሎስ ከጌታ የተቀበለውን መልዕክት አስተላለፈ። “But if anyone does not recognize this, he is not recognized.” (ASB)
ይኼ የ አዲሱ ኪዳን ነቢይነት ከልሳን ሥጦታ ይልቅ የማነጽ አቅሙ ስለተመሰከረለት በሁሉም አማኞች ተፈላጊ የሆነ የጸጋ ሥጦታ መሆን እንደሚኖርበት ሐዋርያው አሳስቧል። “ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ።” (1ቆሮ. 14:1) ይህ ማለት ኤልሳዕና ኤልያስን ኤርምያስና ኢሳይያስን ዳኔልና ሆሴዕን መሳይ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍ ኣለመሆን ነቢይነት አይደለም። አንዳንድ ልዩ የነቢይነት ቅባትና ጥሪ ለሚኖራቸው ሰዎች የተጻፈ ሳይሆን ጸጋው እንደ ዝማሬ፣ እንደ ወንጌል መስካሪነት፣ እንደ አስተማሪነት፣ እንደ አማካሪነት የሚገለጥባቸው ምዕመናን በአካሉ ውስጥ ስለሚኖሩ ነው።
ይህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በሚሠራባት ክርስቶስ በሚከብርባት እግዚአብሔር በሚመለክባት ሕያው በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ሕይወት እስቲንፋስ መኖር ያለበት ጸጋ ነው። የነቢይነት ጸጋ ለኔ ብቻ ስለተሰጠኝ እኔ በምገኝበት ኮንፈራንስ ሁሉ ትንቢት አይጠፋም በቢል ቦርድ ስሙን አስለጥፎ መጥቼላችኋለሁ የሚሉ ዓይነቶችን ልምምዶች በአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ማየት ታላቅ ውድቀት ነው። ከኪሳቸው ፈትለክ አድርገው የሚያወጡ ይመስል “ታላቅ የትንቢት ኮንፈራንስ” ማለት የሚችሉበት ምንም መሠረት የላቸውም።
2. የአዲስ ኪዳን ነቢያቶች ከቤተ ክርስቲያን ሥልጣንና ከቃሉ ሥልጣን በታች ናቸው። መሥራችና ባለራእይ አይደሉም። ባይናቁም ይፈተናሉ። ከተጻፈው ቃል ወይም በውስጣችን ካለው መንፈስ ምስክርነት ጋር ተመዝነው ካላለፉ “ቁጭ በል” ወይም “ውረድ” የሚባሉ ናቸው። እርግጥ የብሉይ ኪዳን ነቢያቶች አንዳች ስህተት ከተገኘባቸው ይወገራሉ እነዚህ ግን ይወገዛሉ። ሰሞኑን ጴንጤቆስጤያዊ ነን የሚሉ አንዳንድ ወገኖች (ነን የሚሉ ያልኩበት ምክንያት የሆነውን ጌታ ነው የሚያውቀው “ብዙ ተዳቅለናል” ለማለት ነው።) አጋቦስ የተባለውን ሰው በመጥቀስ የብሉይ ኪዳን ነቢይነትና የ አዲስ ኪዳን ነቢይነት መንቲያ እንደሆኑ ለማስመሰል ሲሞክሩ ተመልክቻለሁ። “ትንቢተ አጋቦስ” ወይም “የ “አጋቦስ ወንጌል” የተጻፈ ሁሉ እስኪመስል ታላቅ እውቅና ሰጥተው ስሰማ ገርሞኛል።
#ማዕከላዊና_የዳር_ትምህርቶች
#Central_and_peripherial_doctrines
ከተሀድሶ በተገኙ የወንጌል አማኞች መሀል እናራግባቸው፣ እንለያይባቸው፣ እንጣላባቸው ካልን የሚለያዩ ትምህርትና ልምምዶች አሉን፣ ነገር ግን አብረው እየኖሩ ያሉ ልንታገሳቸው የሚገቡ ስነመለኮታዊና ቤተእምነታዊ አተያዮች በርካታ ይመስሉኛል።
ሰሞኑን በዚሁ ሚዲያ የቆሙ (ዛሬ የማይሰጡ) የፀጋ ስጦታዎች አሉ ወይስ የሉም የሚል ምልልስ የትንቢትን ስጦታ ዋነኛ የንግግር ማዕከል በማድረግ መነጋገር ብቻ ሳይሆን መወራረፍ፣ መፈራረጅ፣ ኩነናና አንዱ አንዱን የበለጠ ተጠያቂ ለማድረግ መሯሯጥ እያየሁ እየገረመኝ ነው።
ልዩነቱን እናጡዘው፣ ይህን ያን ከሀዲ እንበል ካልን ጥምቀትንም፣ የአስተዳደር አይነትንም፣ ከደህንነት ጋር ተያይዞ የእግዚአብሔርን ሉዐላዊነትና የሰውን ሀላፊነትንም፣ ከጌታ መምጣት ጋር የሚሰሙ የተለያዩ አተያዮችንም ... እያነሳን መተጋተግ ልንቀጥል ነው፣ ይሄን ያን የስህተት አስተማሪ ነው፣ ከእርሱ ተጠበቁ/ከእርሷ ተጠበቁ ልንል ነው ማለት ነው። ጉድ እኮ ነው!
ምንም እንኳን የየራሳቸው ታሪካዊ አመጣጥና ቤተእምነታዊ አቋም ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ ያሉ የወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ከልምምድ አንፃር Charismatic ናቸው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። Classical Pentecostal የሚባሉትም ወደ ካሪዝማዊነቱ እያጋደሉ ይመስለኛል (በልሳን መናገር በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት/የመጠመቅ ምልክት ነው፣ ሁሉም አማኝ ተሞልቶ/ተጠምቆ በልሳን መናገር አለበት የሚል የዘንድሮ ጰንጠቆስጤአዊ ቤተእምነት ወገን አልገጠመኝም)።
ምን ለማለት ነው መሰላችሁ እምነቶችም ልምምዶችም በታሪካዊ ሂደት ይፈተሻሉ። ተሀድሶ የሚመሰገን ገፅታ ቢኖረውም ጥሎ ያለፈውን ጠባሳ ክርስትና ተሸክሞት ይኖራል፣ Cessationism በክርስትና ታሪክ ረጅም ሂደት ነበረው ከ1900 አካባቢ ጀምሮ ግን በይፋዊ ጰንጠቆስጤአዊ እንቅስቃሴ መጀመር የሚጠየቅና የሚፈተሽ ሆነ፣ ብዙ ቤተ እምነቶች ቢያንስ በኢትዮጵያ ጰንጠቆስጤአዊ ባይሆኑ እንኳን ካሪዝማዊ ሆነዋል። አሁን ደግሞ ሂደቱ ሌላ ተግዳሮቶ አምጥቶ "ሐዋርያዊና ነቢይ" መር የገዢነት (Dominion) ስነመለኮትን ከጀርባው ያደረገ የብልፅግናና የጤንነት ትምህርትን የሚያሰርፅ እንግዳ እንቅስቃሴ እራሱን ተሀድሶ ብሎ የወንጌል አማኙን በሚፈታተንበት ጊዜ ጥቂቶቹ የእቅበተ እምነት አገልጋዮቻችን እቅበተእምነትን ወደ ቤተእምነታዊነት በማውረድ የእርስበርስ መራራ ዕቀባ መጀመራቸው ምን ሊጠቅም ነው?
ስነመለኮት ትምህርትንና ቀደምት መነሻ ቋንቋዎችን እስካፍንጫቸው የታጠቁት ምሁራንም (doctrines ዳንዶቻችሁ እዚህ ውስጥ ትመደቡ ይሆናል) በነኚህ ጉዳዮች አንድ አይደሉም እና እኛ በፌስቡክ እሰጥአገባ ምልልስ መስመር ልናስገባው መሆኑ ነው? ስንቱንስ አሳመንን ይሆን? ደግሞም ክርስትና የግድ ልንስማማባቸው የሚገቡ ዋነኛና ልንታገሳቸው የሚገቡ ተጨማሪ ትምህርቶች እንዳሉት በማሰብ ዋና ባልሆነው መጣላት አግባብ ነው?። መቸስ የኢየሱስን አምላክ-ሰውነትና ብቸኛ አዳኝነትና ልሳን መናገር ዛሬ አለ የለም ሙግትን እኩል ሚዛን ያላቸው ማዕከላዊ ጭብጦች ናቸው አትሉኝም።
ወዳጆች ሆይ ይህ የፌስቡክ እሰጥአገባ ለወንጌል እንቅፋት ቢሆን እንጂ ለአማኙም ቢሆን ጠቃሚነቱ አልታየኝምና ትንሹ ወንድማችሁ ተው ልበላችሁ።🙏
መጋቢ ተስፍዬ ገመቹ
የማይለወጠው/ አይለወጤው እግዚአብሔር
እግዚአብሔር አይለወጥም ማለት በማንነቱ፣ በዓላማውና በሚገባው ተስፋ አይለወጥም ማለታችን ነው። (መዝ 102 ፡25-27)
ምድርና ሰማይ፦ የእጆችህ ሥራ፣ ይጠፋሉ፣ ትለውጣቸዋለህ፣ ይለወጡማል
አንተ፦ ያው ነህ - ሁሉን ነገር ለልዩ ልዩ ለውጥ ይዳርጋል፣ እርሱ ግን ለማንኛውም ለውጥ አይዳረግም - ሚልኪያስ 3:6 እንደጠፋችሁ አታስቡ ይላል። ለምን? “እኔ አልለወጥም” ነገር ግን ያላችሁበትን ሁኔታ ግን እለውጣለሁ ይላል።
በዚህ ዓለም ላይ ከለውጥ ከራሱ በቀር ቋሚ ነገር የለም ሁሉ ነገር ይለወጣል። እርሱ ብቻ አይለወጥም። በዓላማውም በሚገባውም ተስፋ አይለወጥም - ዓላማውም በጎ ነው ተስፋውም ተፈጻሚ ነው።
እግዚአብሔር አይለወጥም ስንል፣ ጸባዩም ኅልውናውም፣ ያላቸው ፍጹምነት በጊዜ ብዛት፣ ኋላ ቀር አይሆኑም፣ ወይም በጊዜ ማነስ የማይበቃ አይሆንም - ሁልጊዜ አዲስ ነው፣ ሁልጊዜ ይበቃል። ዓላማውም ፍጹም ስለሆነ በመሻሻልም ሆነ በማርጀት አይለወጥም፣ እርሱ በምንም ነገርና በማንም ተደራጊም አይደለም፣ ሁልጊዜ አድራጊ እንጂ፣ በዚህም ልክ ማንም እና ምንም የለም! ኢሳ 46:9-11
9 ፤ እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። 10 ፤ በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። 11 ፤ ከምሥራቅ ነጣቂ ወፍን፥ ከሩቅም አገር ምክሬን የሚያደርገውን ሰው እጠራዋለሁ። ተናግሬአለሁ፤ እፈጽማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ። እርሱ በሚገባው ተስፋ አይለወጥም - አንዴ ተስፋ ከገባ ለዚያ ተስፋ ታማኝ ነው ይፈጽመዋል። ምን ብሎናል? ምኞታችንን አዳምጠን ባይፈጸም ከእርሱ አንቀያየም፣ ባለበት ፈልጉት አታጡትም።
ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?” ዘኍ 23:19 ንፅፅሩ ተለዋዋጭ ከሆነው የሰው ልጅ ጠባይ ጋር ነው። ደግሞም “ሳሙኤልም። እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት፤ የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው።” 1ሳሙ 15:29 የባህሪ ለውጥ የታየው በሳዖል ላይ ነው፣ እግዚአብሔር ወደ ሳዖል አይወርድም፣ ሳዖል ግን ከከፍታው ወርዷል።
ሰዎች ለእኛ ያላቸውን አስተሳሰብ ወይ ከእኛ መለወጥ አለበለዚያም ከሁኔታዎችና ከራሳቸው መለወጥ የተነሳ ይለዋውጣሉ፣ ስለዚህ በጠበቅናቸው እናጣቸዋለን። ነገር ግን እኛ ከእርሱ ሐሳብ ስንርቅ፣ ወይ ደግሞ ወደ እርሱ ሐሳብ ስንቀርብ እንለወጣለን እንጂ እግዚአብሔር ከዘላለም አንስቶ ለእኛ ያለው ሐሳብ ግን አይለወጥም።
የእግዚአብሔርን መልካምነት በማሰብ ልናገኘው ብንፈልግ፣ ጠብቀን መልካም የሆነ እና ለእርሱ የሚመቸው ጊዜ ፈልገን አይደለም የምናገኘው፣ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የእኛ ሙድ ነው። ወደ እግዚአብሔር ለጸሎት በምንቀርብበት ጊዜም “ዛሬ ተበሳጭቶ ይሆን? ጠባዩ ተቀይሮ ይሆን እያልን አንሰጋም። አይለወጥም፣ ለዚህ ነው በቋሚነት እርሱ የሚያዋጣን!
በፊቱ የምናደርገው የጸሎትና የዝማሬ ቆይታም እርሱን የመለማመጫና ጸባዩን የመግራት ስልት ሳይሆን የአምልኳችን መግለጫ ነው። አንዳንዶች ወደ ክርስትና ከመምጣታቸው በፊት ከነበሩበት ሃይማኖት የተነሳ አስቀድሞ አማልክትን ለማስደሰት ከሚደረጉ ልማዶች ጋር ያያይዙታል።
የበአል ነቢያትና የኤልያስ የእግዚአብሔር ሰው ፉክክር ይህንን ያሳየናል። እነዚያ የአህዛብ ነቢያት አምላኮቻቸውን ብዙ ተለማመጡ እርሱ ግን የማይለወጠውን የእስራኤል አምላክ ሳይጨነቅ ጠራው በእሳትም መለሰለት።
ትናንት ያዩን የፍቅር ዐይኖቹ ዛሬም አይለወጡም፣ እርሱ በዐመት 365 ቀናት፣ በቀን 24 ሰዓታት ያገኘናል፣ አይለወጥም ይለውጣል።
ለኅጢአት ያለው ጥላቻና ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር የድሮው ከአሁኑ፣ የአሁኑም ከሚመጣው አይለወጥም። ኅጢአታችንን ይጠላል እኛን ይወደናል፣ ስለእኛ ሲል ኅጢአትን አይወድም የማንነቱ ባሕርይ አይፈቅድለትም። በኅጢአታችን የተነሳ እኛን አይጠላንም ይልቁን ጠላቶች ሳለን በማይለወጠው ፍቅሩ ሞተለን።
ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ሮሜ 5፡9-10
ወደማይለወጠው መለስ እንበል!
መጋቢ ሰሎሞን ጥላሁን
አዎን! ነቢያት ዛሬም አሉ!!
ከሰሞኑ ወንድማችን ዘላለም መንግስቱ ነቢያትን በተመለከተ ያነሳው ጥያቄ ትልቅ መወያያ ርዕስ ሆኗል። እውነት ለመናገር "አዝኛለሁ" ብዬ የለጠፍሁት የምሬን ነበር። ምክንያቱም የሃሳዊያኑን መንደር ግር ግር እና "የነቢይ ነቢይ" ጨዋታ እንኳን ትተን "ጤነኛ ናቸው" ብለን ከምንቀበላቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል ካሉ "ነቢያት" መካከል ድፍር ብለን አንድ ሰው መጥቀስ ባለመቻላችን አዝኛለሁና። ሌላው የእኛን ድካም (የጴንጤቆስጤዎቹን) ለመሸፈን ወንድማችን ዘላለምን "የመንፈስ ቅዱስ አሰራር ተቃዋሚ" አድርገን "ለማሳቀል" መሞከራችንም ሌላው የሃዘኔ ምክንያት ነበር።
የሆነ ሆኖ የእኔን አቋም ለጠየቃችሁኝ "ነቢያት ዛሬ አሉ?" ለሚለው ጥያቄ አዎ አሉ። "የወደፊቱን ሊናገሩ ይችላሉ?" አዎ ይችላሉ ነው አጭር መልሴ። በዚህ ከወንድሜ ዘላለም በጥቂቱ የተለየ አቋም ነው ያለኝ። (በርግጥ እርሱ ነቢያት በጥቅሉ የሉም ባይልም) በዚህ ጉዳይ ከእኔ የተለየ አቋም ስላለው ግን "የመንፈስ ቅዱስ የፀጋ አሰራር ተቃዋሚ!" ብዬ አላወግዘውም። ሃሰትንና ሃሳዊያንን በመከላከልና ቤተክርስቲያን እንድትታነፅ በመልፋት ጉዳይ ከእኔ በላይ የሚተጋ ወንድም ነውና። መቼም ያለ መንፈስ ቅዱስ የፀጋ ሥራ እስከዛሬ ድረስ በዚህ ስራ ፀንቶ መቆም አይችልም። በእርሱ ስለሚሰራው ፀጋ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።
የመጨረሻው ዘመን ምልክት
ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ መውረድ በተገለጠው "በልሳን የመፀለይ ስጦታ" ምክንያት በዙሪቸው በነበረው ማህበረሰብ መካከል የተፈጠረውን ግርታ ለማጥራት መነሻ አድርጎ የወሰደው ትንቢተ እዮኤል ምዕራፍ ሁለትን ስለሆነ ከዚያ ብንጀምር መልካም ነው።
እንዲህ ይነበባል "እግዚአብሔር ይላል፦ በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ” (ሐዋ 2፥17) በጴጥሮስ ገለፃ መሰረት ይህ የመንፈስ ቅዱስ መውረድና ስጦታን የመስጠቱ ጉዳይ የመጨረሻው ዘመን "ምልክት" ነበር። ከስጦታው ጋር አያይዞ "በመጨረሻው ዘመን" የሚል ቃል ተጠቅሞ ነበርና። በዚህ መጨረሻ በተባለው ዘመን ከተሰጡት ስጦታዎች አንዱ ደግሞ "ትንቢትን የመናገር" ስጦታ ነው።
በኤፌሶን ምዕራፍ አራት ላይም "ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ" ብሎ ስጦታዎቹን ሲዘረዝር አንዱ የተጠቀሰው "ነቢያት" የሚለው ቃል ነው።
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ” (ሐዋ13፥1) ይላል ቃሉ።
ይሁዳና ሲላስም "ነቢያት" ነበሩ ይላል። አጋቦስ የሚባልም "ነቢይ" እንደነበረ መፅሐፉ ይናገራል። እንዲህ እያልን ብንዘረዝር ብዙ እናወጣለን።
ትንቢት እና ነቢያት
"ትንቢት የተናገረውን ሁሉ ነብይ እያልን መሰየም የለብንም ነቢያት ግን ትንቢት ይናገራሉ" የሚል አባባል አለ። ይስማማኛል። ምክንያቱም በአዲስ ኪዳን መፅሐፍትም ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች ላይ "ትንቢት የመናገር" ስጦታ ተጠቅሶ እናገኛለንና። እንዲያውም ሁሉም አማኝ ሊፈልገው የሚገባ ስጦታ እንደሆነ ለማመልከት "ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ" ይላል (1ቆሮ 14:1)። ደግሞም ጳውሎስ በዚሁ አውድ ውስጥ (1ቆሮ 14: 22-32) ትንቢት የሚናገሩ ሰዎች በጉባኤ እንዳሉ ይጠቅስና "ነቢያት ሁለት ወይም ሶስት ሆነው ይናገሩ ብሎ "ትንቢት" ተናጋሪዎቹን "ነቢያት" ብሎ ይጠራቸዋል። በርግጥ እነኝህ ሰዎች የወደፊቱን ይናገሩ ያለፈውን በዚህ ክፍል ላይ የተገለጠ ነገር የለም። ነቢያት ግን ትንቢት ይናገሩ ነበር።
የአዲስ ኪዳን ነቢያት የወደፊቱን ይናገራሉ?
በርግጥ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ነቢያት ከመሲሁ መምጣትም ይሁን ከእስራኤል ሁኔታ አንፃር ስለወደፊቱ ቢናገሪም በአብዛኛው ግን ህዝቡን ወደ ህጉ እንዲመለስ ከማሳሰብ አንፃር ነበር ትንቢት የተናገሩት። በአዲሱ ኪዳን የምናገኛቸውም ነቢይ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አገልጋዮች ለምሳሌ ይሁዳና ሲላስ አገልግሎት በመምከርና በማፅናት ነበር "ነቢይነቱ" የተገለጠው የተገለፁት “ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው።” (ሐዋ 15፥32) እንዲል ቃሉ።
ነገር ግን ደግሞ በዚሁ በአዲስ ኪዳን "ነብይ" ተብሎ የተጠቀሰውን አጋቦስን ብንወስድ ሁለት ጊዜ የወደፊታዊ ትንቢቶችን ተናግሯል። "ጳውሎስ በኢየሩሳሌም መከራ እንደሚደርስበት" (ሐዋ 21:10) እና "በምድር ላይ ረሃብ እንደሚመጣ" (ሐዋ 11:28) እነዚህ ሁለቱ ትንቢቶቹም ተፈፅመዋል። ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን ነቢያት አሉ፤ ትንቢትም ይናገራሉ! የሚለውን ያፀናልናል። ስለዚህ ነቢያት ወደ ቃሉ እንድንመለከት፣ እንድንፀና እና ቤተክርስቲያን እንድትታነፅ የአሁኑንና ያለፈውን ይናገራሉ። ልክ እንደ አጋቦስ ደግሞ የወደፊቱንም ይናገራሉ።
ስለዚህ በሐዋ 2 "ትንቢትን መናገር" (ሌሎቹ ስጦታዎች እንዳሉ ሆነው) የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደሆነ ከተገለፀበት የጴጥሮስ ንግግር በኋላ ይህንን እውነት የሚያፀና እንጂ የሚቃወም ወይም ይህ ስጦታ መቆሙን የሚገልፅ ምንም ዓይነት ትምህርት በቃለ እግዚአብሔር ውስጥ ስለሌለ "ትንቢትን የመናገር ስጦታ" ዛሬም ድረስ ያለ "የመጨረሻ" የተባለው ዘመን እስኪጠናቀቅ እና ስጦታው የተሰጣት ቤተክርስቲያን በምድር እስካለች ድረስ የሚቀጥል የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው ማለት ነው። ሁላችንም እንደምንገነዘበው እና ቃሉ እንደሚያስተምረን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከወረደባት ቀን የጀመረው ይህ "የመጨረሻው ዘመን" የሚባለው ዘመን ገና አልተፈፀመምና።
ነገር ግን "ሌሎችም ይለዩዋቸው" እንደሚል የሚነገሩ ትንቢቶች ሁሉ ይመዘናሉ። በዚያ ዘመን እነጳውሎስ ካስተማሩት አንፃር ተመዝነዋል። ዛሬ ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስ እጃችን ላይ ስላለ ከቃሉ አንፃር ይመዘናሉ። ከቃሉ ትምህርት ከወጡ ይወገዛሉ ሃሳዌ ነቢያት ናቸውና።
በመጨረሻም
መፅሐፍ ቅዱስ የፀና የትንቢት ቃል ነው? እውነት ነው። ነቢያት ዛሬም አሉ? ቃሉ ያስተምራልና አሉ! እውነት ነው። ያለፈውንና የአሁኑን ይናገራሉ። ይህም እውነት ነው። የወደፊቱንም ይናገራሉ። ይህም መቶ በመቶ እውነት ነው። ታዲያ ዛሬ በኢትዮጵያ አብያተክርስቲያናት መካከል (ሃሳዊያኑን ሳንቆጥር) እንዲህ አይነቶቹ "ነቢያት" አሉ ወይ? ከሆነ ጥያቄው የእኔ መልስ "አላውቅም" የሚል ነው። ነገር ግን በህይወቴ እና በትዳሬ በአገልግሎቴም የተነገሩና የተፈፀሙ ትንቢቶች ግን እንዳሉ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ስለ እነኚህ "ነቢያት" መሉ ለሙሉ በአደባባይ ለመመስከር ግን ጊዜ ያስፈልገኛል። ተባረኩ!
ለመውጫ
ከወንድሜ ዘላለም መንግስቱ ጋርም ሆነ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የእርሱን ሃሳብ ከሚጋሩ ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር በዚህ ጉዳይ ያለን አመለካከት የተለያየ ቢሆንም በእግዚአብሔር መንግስት ስራ በተለይም ወንጌልን ከሃሳዊያን ለመከላከል አብረን መስራታችንን እንቀጥላለን!
ቴዎድሮስ ተጫን
ወደ ቀልባችን እንመለስ!
እውነት . . . እውነተኛ ነቢያት በዚህ ዘመን አሉ?
እውነተኛ ነቢያት በዚህ ዘመን አሉ? በሚል ርእስ ጽሑፎች ያካፈልኩትና ቪድዮም የሠራሁት ከ5 ዓመታት በፊት ነው። ትንቢትን በተመለከተ፥ ትናንት የለጠፍኩትን፥ ማለትም፥ ወደፊታዊውን ትንቢት በተመለከተ ትክክለኛውን ነገር የነገረን ቅዱስ ቃሉ ብቻ መሆኑን እና ያንን ቅዱስ ቃሉ የነገረንን ነገር በመረዳት ወደፊት የሚሆነውን ነገር መተለምና መጠበቅ እንደምንችል የጻፍኩትን የጻፍኩትን ትናንት ሳይሆን ከዓመታት በፊት ነው። ከ25 ዓመታት በፊት በመንፈስ ቅዱስና ካሪዝማዊ ቀውሶች ውስጥ ብዬዋለሁ። ይህ አሳብ በቀጥታ የተወሰደውም ከ5 ዓመታት በፊት ካካፈልኩት ቪድዮ ነው። ቪድዮው እዚህ ይገኛል፤ https://www.youtube.com/watch?v=tmB2pq071EU
እዚያ ስለ cessationism ምንነትና የጸጋ ስጦታዎች ተቋርጠዋል ባዮች cessationistቶች ምን እንደሚሉና ይህ ትምህርት የተሳሳተ መሆኑንም በግልጽ አስተምሬአለሁ። እርግጠኛ የሆንንበት ወደፊታዊ ትንቢት ያልኩት የጌታችን ዳግም መምጣት እና ከመምጣቱ በፊት የሚሆኑት ነገሮች ንድፍ ነው። ይህንን እርግጠኛ ሆነን እናውቃለን። እንዲፈጸምም እንጠብቃለን። ይህም ደግሞ፥ ቤዛችንና አምላካችን የሆነው ጌታ አንድ ቀን ወደ ፊት እንደሚመጣ እንጂ፥ ‘መጋቢት 13 ቀን 2028 እመጣለሁ’ አላለም። ቢል ኖሮ በጣም ጥሩ የሚመስላቸው አሉ። ግን በጣም መጥፎ ነበር። እርሱ ያላለውን በእርሱ ስም መቼ እንደሚመጣ የነገሩን ብዙ ሰነፎች በታሪክም በዘመናችንም ኖረዋል።
በዚያ ቪድዮ ስለ ጅምላ ተንባዮችም ተናግሬአለሁ፤ ከዘማሪ ደረጀ ሙላቱ ግጥምም፥
ነቢይ ነኝ ያሉትን ሰብስቡና አምጡ፤
ስለ ቀጣዩ ዓመት ተገቢ ድምጽ ይስጡ፤
ጅምላ ትንቢት ሳይሆን ክስተትን ይግለጡ፤
አለዚያ ባሉበት ሹመቱን ቁረጡ!
የምትለዋን ስንኝ አካፍዬ፥ የነቢያት ነን ባዮቹ ወደፊታዊ ትንበያዎች ተሰብስበው የማይፈጸሙቱን ተስፋዎች የሚናገሩት ‘ነቢያት’ ሹመት የሚቆረጥ ቢሆን በአንድ ዓመት ውስጥ በሙሉ ይወርዱና እንደገና እስኪሾሙ ትንሽ ከወደፊታዊና ግምታዊ ትንበያ እርርፍ ይባል ነበር። ብያለሁ። ትናንት ያካፈልኩት ስለ ወደፊታዊ ትንበያ ነው። በዚያ ቪድዮ ትንቢትን በስፋት በመተርጎም አንዱ የትንቢት ትርጉም ገጽታ ወደ ፊት የሚሆነውን መናገር ማለት መሆኑን ተናግሬ፥ ይህንን ወደፊት የሚሆነውን በግምትና በነሲብ ሳይሆን በቀጥታ የሚነግሩን አለመኖራቸውንም ተናግሬአለሁ።
በዚያ ቪድዮ ትንቢት ሦስት ነገሮች ነው ወይም ሦስት ትርጉሞች አሉት ብያለሁ። አንደኛው፥ ይህ እዚህ የምናገርበት ወደፊታዊው ትርጉሙ ነው። በቃሉ ውስጥ ያየናቸው ነቢያት ስለ ወደፊቱ ብዙ አልተናገሩም። የተናገሯቸው ተፈጽመዋል፤ ገናም ይፈጸማሉ። አሁንም ይህንን ነገር ልድገመው። እንዲያውም ያኔ እዚያ ከተናገርኩት አንድ አንቀጽ ቃል በቃል ወስጄ እዚህም ልጻፈው፤
". . . ነገር ግን፥ ነሲባዊ ትንበያዎች እና በእውቀት የተደገፉ ግምቶች (educated guesses) ትንቢት አይደሉም። መባልም የለባቸውም። ለግለ ሰቦች አዎንታዊ ንግግር መርጨትም ትንቢት አይደለም። ስለዚህ ወደ ፊታዊ ትንበያዎች፥ ለምሳሌ፥ ‘ጌታ በዚህ ዓመት መስከረም 28 ማታ ይመጣል፤ ወይም ጥር 14 ቀን ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤ ወይም በአሁኑ የአሜሪካ ምርጫ ሂለሪ ክሊንተን ታሸንፋለች፤’ ‘በሚቀጥለው ግጥሚያ የማንችስተር ቡድን ያሸንፋል፤’ ወይም፥ ‘በሚቀጥለው ዓመት እዚህ አገር ትሄዳለህ፥ ታገባለህ፥ ትወልጃለሽ፤’ ወዘተ፥ የመሰሉ ትንቢቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገልግሎቶች አይደሉም። ነሲባዊ፥ ግምታዊ፥ ጥንቆላዊ ናቸው። በዚህ ጉዳይ ወይም እንደዚህ ስላለው ወደፊታዊ ትንበያ ሴሴሽኒስቶች ከሚሉት ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። ነሲባዊ፥ ግምታዊና ጥንቆላዊ ትንበያዎች አለመፈጸማቸው ሲረጋገጥ ተንባዮቹ ሐሰተኛ ነቢያት መሆናቸው መረጋገጡ በመሆኑ ከዚያ በኋላ እነዚያ ነቢያትነን ባዮች መገለጥና መወገዝ፥ ከአገልግሎትም መፍፋቅ አለባቸው። እንዲህ ያሉ ተንባዮች ተባዮች ናቸው። ‘ነቢያት 100% ትክክል እንዲሆኑ መጥጠበቅ የለበትም’ በማለት ለሰይጣናዊ አሠራር እና ተንባዮቹን ከተጠያቂነት በነጻ እንዲያፈተልኩ በር መክፈት የሐሰተኞችን እጅ ማበርታት ነው፤ አሳዛኝ አሳችነት ነው። ለሐሰተኛ ተንባዮች በር መከፈት የለበትም።"
በአዲስ ኪዳን ውስጥ አሁን በዓለማችንና በተለይ በአገራችን እንደምናያቸው ያሉ የግምት ተንባዮች አልነበሩም። በተለይም ስኬትና ገንዘብ፥ ሚስትና ባል፥ ቤትና መኪና፥ አዱኛና ድሎት፥ ብርና ካርድ፥ ሌላም ቅራቅንቦ የሚተነብዩ ተንባዮች አልነበሩም። ዛሬ ቢከሰቱ ሐሰተኛ ነቢያት ለምን አንላቸውም?
ሁለተኛ፥ ትንቢት ስላለንበት፥ ስለ አሁኑ መናገር ነው። የትኛውንም የትንቢት መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከፍተን እንይ ከ85-90 በመቶው ስለነበሩበት ዘመን የተነገረ ነው። አንዳንዱማ 99 በመቶ ማለትም ይቻላል፤ ለምሳሌ ትንቢተ ዮናስ። ስላለንበት ሁኔታ፥ መበረታታት ባለብን የብርታት ቃልን፥ (በዕዝራ ውስጥ እንደምናየው ሐጌ) በድፍረት መናገር፥ በልበ ሙሉነት፥ ከቃሉ በመነሣት ውድቀታችንንና ዝቅጠታችንንም፥ መተላለፋችንንና መበደላችንንም፥ ዝምታችንንና አመቻማችነታችንንም መናገር ትንቢትን መናገር ነው። ለስግብግብ ልባችን አሞሌ የሚጥሉልን ሳይሆኑ ለክተውን ልካችንን የሚነግሩን ከኖሩ በመካከላችን ነቢያት አሉ።
ሦስተኛ፥ ትንቢት ማለት ቅዱስ ቃሉ ነው። ቃሉን መስበክ ትንቢት መናገር ነው። እውነተኛ የቃሉ ሰባኪዎች ነቢያት ናቸው። በቃ፤ በአጭሩ፥ ቃሉ ትንቢት ነው፤ የቃሉ አስተማሪዎችና ሰባኪዎች ነቢያት ናቸው።
እውነት፥ ከዓመት በኋላ የሚሆነውን የሚያውቁ ተንባዮች በአገራችን በ2 ዓመት ሦስት ዙር ጦርነት እንደሚኖር እና ብዙ 10 ሺህዎች (በአንዳንዶች ግምት መቶ ሺህዎች) እንደሚያልቁ ነግረውን ነበር? ከስድስት ወራት በኋላ የሚሆነውን የሚያውቁ ተንባዮች ከ3 ወር በኋላ ኮሮና አገራችንን ብቻ ሳይሆን ምድርን በሙሉ ዝግት፥ ዝግትግት እንደሚያደርግ ያውቁ ነበር? ከ3 ወር በኋላ ያልኩት በኅዳርና ታኅሣስ ሁሉ ሊዘጋጋ እነሱ፥ የፍንዳታ ዓመታችን፥ የመጠርመስ ዓመታች፥ የከፍታ ዓመታችን፥ የእንትን ዓመታችን እያሉ ይዘባነኑ ስለነበር ነው። ያኔ እንዳደረጉት የበተስኪያን ጃንጥላ የመሰለ ዩኒፎርም እየለበሱ ኬክ እየቆረጡ ይቀባቡ ነበር? ያኔ እኮ፥ ኮሮና በር ላይ ቆሞ ሊያንኳኳ እጁን እያነሣ ነበር። ማን ነበር ያየው? ሐሳውያኑ ሁሉ ከኛ ጋር እኮ አብረውን ነው ያዩት።
እባካችሁ፥ ወደ ቀልባችን እንመለስ!
ዘላለም ነኝ።
መከራ ጫፋችሁን አይነካችሁም የሚል ጌታን አልተከተልንም። እንደውም «መከራን የሚቀበሉ ብፁአን ናቸው» ብሎናል። እንደ ሰው የሚደርስብን መከራ አያሌ ነው። የሚያደርስብን ስጋዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳትም ቀላል አይደለም። ሕይወትን የሚያከብድ ብዙ ፈተናና መከራ በዙሪያችን አለ ወደ ፊትም ደግሞ ይኖራል። በህይወት ጎዳናችን ላይ በርከት ያሉ እንቅፋቶች እየመቱን እንገጣጠባለን።
.
መከራ ለምን እንደሚደርስብን የማወቅ ጉጉት ቢኖረንም ብዙ ጊዜ ምክንያቶቹን ማስረዳት የማንችልባቸው ወቅቶች ይኖራሉ። መዝሙር 44ን ለዚህ ሁነኛ አስረጂ ነው። አባቶች ያሸነፉትና የተዘለሉት በክህሎታቸው እንዳልነበር የሚያወሳው ዝማሬ የእግዚአብሔርን እርዳታ ብቸኛው ምክንያት መሆኑን ይናገራል። ዘማሪው እግዚአብሔር ላይ ያለውን መታመን በማንሳት በራሱ ችሎታና አቅም አለመመካቱን «በቀስቴ አልተማመንም፤ ሰይፌም አያስጥለኝም።» (ቁ.6) በማለት ትምክህቱን ይጠቁማል። ነገር ግን ልናስረዳው የማንችለው ከባድ መከራ ደርሶብናልም በማለት ጥያቄ ያነሳል። ለምን መከራ ደረሰብን ብሎ ማስረጃ ከመጠየቁ በፊት ዝማሬው እርዳታና ተማጽኖ በማቅረብ ዝማሬውን ይቋጫል።
አንዳንዴ 'ይህ መከራ ለምን?' ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ መሻት ከተዋላጅ ሰበቦች ይመነጫል። ምክንያቱን አለማወቅ የመረሳትና የመተው ስሜትን ማምጣቱ አንደኛው ነው። (መከራችንንና መጠቃታችንን ለምን ትረሳለህ? መዝ 44:24) 'ይሄ ሁሉ የሆነው ብተትወኝና ብትረሳኝ ነውና ቶሎ እየሆነ ያለው ነገር ንገረኝ' ብሎ ይሞግታል። ምክንያቱን ማወቅ በሚያልፍበት መከራ አላማን የሚያገኝ ይመስለዋልና።
ሲ. ኤስ. ሉዊስ የመከራን አላማ ከአንድ መልካም ሰርጅን ስራ ጋር ያቆራኘዋል። ሰርጅኑ ጎበዝ ባለሙያ ከመሆኑ የተነሳ በደንብ እየቀደደ ወደ ታማሚው አካል ይደርሳል። ነገር ግን መስተካከል ወዳለበት የሰውነት ክፍል ሳይደርስና ቀደ ጥገናው ሳይጠናቀቅ ስራውን ቢያቆም ቀደም ብሎ ያደረገው ነገር በሙሉ ከንቱ ይሆናል።
.
አንዳንዱን ህመምና ስብራት ከጌታችን በቀር የሚያውቀው የለም። 'ማንም አያውቀውም ያየሁትን ችግር/ ከጌታ ኢየሱስ በስተቀር' የተባለው ተወዶ አይደለም። ፍጹም ሰው ፍጹም መለኮት ሆኖ በአርያም ስላለ ህመማችን ይገባዋል። መከራችንን ተካፍሎታል። ጌታችን ጠባሳ ስላለው ጠባሳችንን ይረዳዋል። በስጋው መከራን ስለተካፈለ በሚደርስብን ማናቸውም መከራ ይራራልናል።
.
በክርስቶስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
1 ጴጥሮስ 5:10
አማኑኤል አሰግድ
በክርስቶስ የቤዝዎት ሞት የቀድሞ ጠላቶች ሁሉ ታርቀዋል፤ የክፍፍል ግድግዳ ፈርሷል። በክርስቶስ አካል ውስጥ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ፣ ወንድ ወይም ሴት የሚል ክፍፍል የለም። ከመስቀሉ ሥራ የተነሣ የክርስቶስ ማኅበረሰብ መታወቂያውም ሆነ ውቅሩ ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ መደብ ወይም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም አይደለም። እነዚህ መለያዎች በሙሉ አንጻራዊ ሆነዋል። ገዢው ፋይዳ እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በፈጸመው ፍጹም የዕርቅ ሥራ የተገኘው ማንነት ነው። በእርሱና በሰው፣ በሰውና በሰው እንዲሁም በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ ለአንዴና ለዘላላም በማፈረስ አንድ አዲስ ሰው ፈጥሯል። “. . . ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል (የማይታረቅ ጠላትነት) ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና” (ኤፌ. 2÷14-15)። አይሁድ፣ አሕዛብ፣ ወንድና ሴት፣ ባርያና ጨዋ አንድ ሆነዋል።
ልዩነት የለም - በምድር ላይ ካሉ ማኅበረሰቦች ሁሉ፣ የክርስቶስን ማኅበረሰብ ልዩ የሚያደርገው ይኸው በመስቀሉ ሥራ ብቻ የተገኘው ማንነት፣ ሰላምና አንድነት ነው። ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሆኗል! “ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተሰብ አባል” የሆነው በክርስቶስ መስቀል ቤዛዊ ሥራ ነው። ይህ እግዚአብሔራዊ ቤተ ሰብነት፣ በየትኛውም መልኩ ወደ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጐራ የማይወርድ ነው።
በበዓለ አምሳ ቀን ከልዩ ልዩ ባህል፣ ነገድና ቋንቋ፣ የተሰበሰበውን ሕዝብ አንድ ያደረገው የሮም ፓለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ወይም ይሁዲነትን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩ ሃይማኖቶች፣ ባህሎችና ማኅበራዊ ዕሴቶች አልነበሩም። መንፈስ ቅዱስ ነበር። የአዲሱ ማኅበረሰብ ገዢው መለያ ከክርስቶስ ዋጆአዊ ሥራ የተነሣ የተገኘው ማንነት ነበር። ሌሎች ምድራዊ የማንነት ልዩነቶች ሁሉ የመለያየት ግድግዳ መሆናው አብቅቷል። ስለዚህ የክርስቶስ ማኅበረሰብ ውበቱ ልዩነቱ ነው። ለእግዚአብሔር ለራሱ የተለየ ሕዝብ በሆነበት ልክ ያህል ብቻ ነው ለሌላው ሕዝብ የዕርቅና ሰላም አማራጭ የሚሆነው።
“አራቱም ሕያዋን ፍጡራን እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ክንፎች ነበሯቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸው በዐይኖች የተሞሉ ነበሩ፤ ቀንና ሌሊትም፦ 'ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረው፣ ያለውና የሚመጣው፤ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ' ማለትን አያቋርጡም። 'ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።'” ( ራእይ 4 : 8 , 11)
“እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ 'መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል። በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ዘመሩ፤ 'የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት፣ ጥበብና ብርታት፣ ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ ሊቀበል ይገባዋል።'”
(ራእይ 5 : 9 , 12 )
በርግጥ ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሆንን፣ የሚገዛንም ዋናው ፋይዳ ደግሞ ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ የተዋጀንበት ማንነት ከሆነ፣ እርስ በእርስም ሆነ ሌሎችን በብሔርተኝነት መነጽር ልንመለከት አንችልም። ከፍ ሲል ያሉትን ሦስት መዝሙሮች (ለነበረው፣ ላለውና ለሚመጣው፤ ሁሉን ለፈጠረው እንዲሁም ፍጥረትን በደሙ ለዋጀው ክርስቶስ የቀረቡ) የአምልኮው መካከል ያደረገ ክርስትናና ዘረኝት አብረው አይሄዱም።
- ተሐድሶ ይሁንልን! አሜን
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
የዛሬ 505 ዓመት፣ በዛሬዋ ዕለት፣ በኦክቶበር 31፣ 1517 አመተ እግዚ አንድ ብዙም የማይታወቅ መነኩሴ በአንዲት ትንሽ የጀርመን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮፌሰር የነበረ ሰው በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ በሚገኘው የቤተ ክርስትያን በሮች ላይ የተወሰኑ ወረቀቶችን ለመለጠፍ መዶሻ አነሳ። እነዚያን ወረቀቶች በቤተ ክርስትያን አደባባይ ላይ የለጠፈበት ምክንያት የቤተ ክርስትያኑ በር/አደባባዩ ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እንደ ማስታወቅያ ሰሌዳ ያገለግል ስለነበር በርከት ያለ ሰው እንዲመለከተውና ውይይት እንዲያጭር አስቦ ነበር።
በለጠፈው ወረቀት ውስጥ 95 አናቅጽት (Thesis) 'የኢንደልጀንስን' [indulgence] (የኃጢአት ይቅርታ ሰነድ) የመሸጥ ልምምድ ከጳጳሱ ፍቃድ ያገኘና አንድ ሰው 'ፑርጋቶሪ' [Purgatory] (ነፍስ ወደ ገነትም ሆነ ሲኦል ከመውረዷ በፊት የምትሆንበት ስፍራ) ውስጥ በምድር በሕይወት እያለ ስላጠፋው ስለሃጢያቱ የሚቆይበትን ጊዜ (ወደ መንግስተ ሰማይ ከመግባቱ በፊት) በሚገዛው 'ኢንደልጀንስ' መቀነስ ይችል ነበር የሚለውን ፀረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ የሚገዳደር ነበር። ይህ 'ኢንደንጀልስ' በወረቀት የሰፈረና የቤተ ክርስትያንን ይሁንታ አግኝቶ መግዛት ለቻለ ሁሉ የቀረበ ነበር። ህዝቡም ኢንደልጀንሱን ይገዛ ዘንድ 'በቅቤ አቅልጥ' ደላላ አሻሻጮች ይጎተጎት ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታዋን ሰጥታ ነበር። ህዝቡ ለራሱ፣ ለዘመዱና ለወዳጁ ይገዛ ነበር፤ በሞቱት ስም እንኳን ሳይቀር ይቸበችቡታል።
ሉተር 95 አናቅጽቱን ጽፎ ሲለጥፋቸው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ባሉት ፕሮፌሰሮች መሃል ውይይት እንዲፈጥር በማሰብ ነበር። ነገር ግን ዘጠና አምስቱ አናቅጽት ከቪተንበርግ ፕሮፌሰሮች ከባቢ በዘለለ በመላው የጀርመን ግዛቶችና በጠቅላላው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ዘንድ ታላቅ ሁካታን ለመፍጠር በቃ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ብዙ ህዝብ የዚህን መነኩሴ ስም ማወቅ ጀመረ፣ በቪተንበርግ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት ዶክተሩን ማርቲን ሉተርን።
ህዝብን በማወክና ባለመታዘዝ ቤተክርስትያን ከሰሰቸው፣ በጀርመን ንጉስ ፊትም ራሱን እንዲከላከልና ያደረገው ሃሰት መሆኑን አውቆ እንዲያስወግድ ታዘዘ። ያደረገው ስህተት መሆኑን ባለመቀበሉና ህሊናው ለቅዱሳት መጽሐፍት ተገዢነታቸውን በማጽናቱ ምክንያት የውጤቱን ስሜት 500 አመታትን ተሻግሮ ዛሬ እኛም ይሰማናል።
.
«ስቻለሁ የምለው አንዳች ነገር የለኝም፤ ኅሊናዬ ከሚያዘኝ ውጪ መሆን ትክክልም ሆነ አግባብ አይደለም። እነሆ፤ እዚሁ ቆሜያለሁ፤ ከዚህ ውጪ ምንም ላደርግም አይቻለኝም። እግዚአብሔር ሆይ እርዳኝ። አሜን።»
.
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንዳሉት፣ "አሕይዎና ተሐድሶ (Revival and Renewal or Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠ ሥርዐት (Establishement) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥዎ ካላቸው ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሐሳቦች ናቸው።" በዚህ ሰው ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በታማኝነት መታዘዝና መሰጠት ምክንያት የቤተክርስቲያን መልክ እንደ ቀደሞው ላይሆን ተለውጧል።
.
ተሐድሶ ብቻ መቆምን ይጠይቃል። ዘመንን መረዳትን፣ መጽሐፍትን መመርመርን፣ ለእግዚአብሔርና ለህሊናችን ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። ተሐድሶ ወደ አባቶችና አያቶች ለመንፀሪያ መመልከትን አንደ ቄንጥ አያይም። የድነትን መኸከለኛ፣ የእምነትን ፈፃሚ፣ የእግዚአብሔርን መገለጥ፣ ትምሕርተ ክርስቶስን አደብዛዥን ሁሉ ለመቃወም ሁለቴ አያስብም። ተሐድሶ ቃለ–እግዚአብሔር ማሕደረ–ክርስቶስ በተባለችው ቤተክርስቲያን ሲደፈጠጥ ጥሪውን በማማ ላይ ያሰማል፤ እነሆኝ ለህሊናዬም ለቃሉም ቆሜያለሁ ይላል። እግዚአብሔር ልጁን በገለጠበት ቃል በኩል ለኅሊናዬ ብቻዬን እንኳን ቢሆን እቆማለሁ የሚል እውነትና ፅናት ያድለን።
.
የዛሬ 506 ዓመት ግድም የተለኮሰውን የተሐድሶውን እሳት ከሰሞኑ አስበን ውለናል። ከተሐድሶው ብቻዎች አንዱና የተሐድሶው ልበ ምት የሆነውን "ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ" የሚለውን ርዕስ አውስተናል።
መልካም እለተ ተሐድሶ ማስታወሻ! የከርሞ ሰው ይበለን!
አማኑኤል አሰግድ
የተሐድሶው ሲታወስ ፕሮግራም ዛሬ 9:00 ላይ ይጀምራል ይጀምራል!
ቦታው ሳር ቤት ሙሉ ወንጌል (ከአዳምስ ፓቪልዮን በተምሳሌት ኪችን የሚያስወርደውን አስፓልት 400 ሜትር ያህል እንደ ተጌዙ ያገኙታል፣ ጎግል ማፕ ለምትጠቀሙ ደግሞ ይኸው ሊንኩ Sarbetoch Full Gospel Believers Church
https://maps.app.goo.gl/bVnz91gV91UaMKAq8 )
ነገ! ቅዳሜ ከ9:00 ጀምሮ!
=====================
በነገራችን ላይ ...
ተሐድሶ ጽዩፍ ነው። ቃሉ ለቆሸሸ አላማ ሲውል፣ ድነት መሃከለኛውን ሲስት፣ ፀጋ ሲራከስ ይጸየፋል። ባህሪው ነው! ታሪክ ትውፊት ስርአት ብለው ቆሻሻ ካባ ደርበው ሲያላዝኑበት በቅዱሱ ቃል ወንፊት ያቀላቸዋል፣ ያጠላቸዋል። ቃሉ ያላሳለፈውን አያሳልፍም፣ ከቃሉ ውጪ ምንም ይሰማ ዘንድ አይወድምና።
ተሐድሶ ተመላሽ ነው.... ወደ መጀመሪያውና ወደሐዋሪያቱ ቤተክርስትያን። ወደ ጤነኛውና መጀመሪያው ይሸሻል፣ ቃሉን ተከትሎ እግሬ አውጪኝ ነው። ተሐድሶ አዲስ ስርአት፣ አዲስ ወግ፣ አዲስ ሃይማኖት ማምጣት ሰንደቁ አይደለም። ምጡ የመጀመሪያውንና የጥንቱን ክርስትና መውለድ ብቻ ነው!
ተሐድሶ አይኑም፣ ልቡም ፈቃዱም ሆነ ፍላጎቱ ያለው የተሰቀለው የሞተው ከሞትም የተነሳው ዳግም የሚመጣው ክርስቶስ ላይ ብቻ ነው። ክርስቶስና ያፈሰሰው ፀጋ ሲደበዝዝ ጉድ እንደሚፈላ ያውቀዋል፣ ከክርስቶስ ውጪ ላሳር ባይ ነው። ከክርስቶስ ውጪ ሁሉ ጨለማ፣ ሁሉ ገደል፣ ሁሉ ሃሰት ነው! ለዚህ ነው ነገረ መስቀሉ ብቻውን መሃከለኛ አስተምህሮዬ ነው ብሎ የሙጥኝ የሚለው።
ተሐድሶ የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋፋ ስርአት፣ ወግ አልያም ግለሰብ ሲነሳ ተቆጪ ነው። በአስተምህሮውም ሆነ በልምምዱ ብቸኛው ክብር የተገባው እግዚአብሔር እንደሆነ ያውጃል። ክብር ለእግዚአብሔር ልበ ምቱ ነው።
አዎ አሁንም ቃሉን የሚክድን፣ ክርስቶስን የሚያደበዝዝን፣ ፀጋውን የሚያክፋፋን፣ የእግዚአብሔርን ክብር አሽቀንጥሮ የሚጥልንና እምነትን የሚበርዝን የትኛውንም ወግና ባህል ስርአትና ልምምድ እንቃወማለን!
#ተሐድሶው_ሲታወስ
አማኑኤል አሰግድ
የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች ነን? እንዴት? የእግዚአብሔር ልጆችስ ነን? እንዴት?
ክፍል አራት
2. የባሕርይ ተካፋዮች
የልጅነታችን ሂደትስ እንዴት ነው የተከናወነው? የእግዚአብሔር ልጆች የሆንነው በተፈጥሮአችን ወይም በፍጥረታችን ሳይሆን እግዚአብሔር እንደ ልጆች አድርጎ ተቀብሎን ነው። ልጅነት የተሰጠን ስጦታ ነው እንጂ ከወላጆቻችን ስንወለድ በተፈጥሮ እንዳገኘነው ያለ መወለድ አይደለም። ቀደም ሲል ካየናቸው ጥቅሶች አንዱ በገላ. 4 የሚገኘው ነው። ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። ገላ. 4፥4-7።
ይህ ጥቅስ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ እና ልጆች እንደሆንን በግልጽ ይናገራል። የእግዚአብሔር ቃል በማያሻማ መንገድ ልጆች መሆናችንን ይመሰክራል። ልጆች ነን። ልጆች የሆንነው ደግሞ ምንም የራሳችን ፍሬ ኖሮን ሳይሆን እግዚአብሔር ልጁን እንዲዋጀን ልኮት በእርሱ የዎጆ ሥራ በኩል ነው ልጆች የሆንነው። እርሱን ስንቀበል ልጆች ሆንን። ልጆች የሆንነው እግዚአብሔር ልጆቹ አድርጎን ነው። እንጂ በልጁ በኩል ከራሱ ጋር ባያስታርቀን ኖሮ፥ በራሳችንማ ጠላቶች ነበርን። ቃሉ ልጆች መሆናችንንም ልጆች የሆንነው በመደረግ መሆኑንም ይነግረናል። እነዚህ ሁለቱ እርስ በርስ የሚጋጩ አይደሉም።
ልጆች የሆንነው ልጆች ተደርገን ተወስደን ነው። ከሆንን እና ከተደረግን፥ አድርጎ የወሰደን አለ ማለት ነው። ልንሆን ተወስነን ከሆነ የወሰነ አለ ማለት ነው። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። ኤፌ. 1፥5። ይህ ቃል አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ቋንቋ υἱοθεσία ሁዮቴሲያ መሆኑንም አይተናል። ልጅ መሆን፥ ልጅ መደረግ፥ እንደ ልጅ መወሰድ ማለት ነው። እኛ በክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔር ልጆች ተደርገናል። ታዲያ ተደርገናል የሚለው ያልበቃቸው ሰዎች ከክርስቶስ ጋር እኩያ የሆኑ ልጆች እንደሆኑ ራሳቸውን ያሳብጣሉ። ልጅነት ሥልጣን ቢሆንም (ዮሐ. 1፥12) በሥልጣናችን የተቀዳጀነው ሥልጣን ሳይሆን የተሰጠን ሥልጣን ነው። ይህንን υἱοθεσία ሁዮቴሲያ የሚለውን ቃል ብዙዎቹ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች the adoption of sons ወይም the adoption of children ብለው ተርጕመውታል። ትክክለኛ ትርጉም ነው። አንዳንድ ሰዎች ማደጎ እና ጉዲፈቻ የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ። ይህ ቃል በአገራችን አሉታዊ የሆነ ምስል ስለሚቀርጽ ለአንዳንዶች ግራ ያጋባል። ያጋባ እንጂ ነገሩ ግን ያ ነው።
በአገራችን ባህል ቃሉ አሉታዊነት የተጫነው ይሁን እንጂ፥ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ዘመንና ዐውድ ይህ ቃልና ልማድ ግን ድንቅ ነገር ነው። በአገራችን ማደጎ ተደርገው የሚወሰዱ ልጆች፥ ችግረኞች፥ አሳዳጊ ያጡ፥ ምስኪኖች፥ ድሀ አደጎች፥ ወላጅ አልባዎች ናቸው። እንደዚህ ብቻ ብንወስደውም እንኳ ትርጉሙ ያስኬዳል። እኛም እኮ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች ከመሆናችን በፊት ምስኪኖችና ከጸጋ የራቅንና ከክብሩ የጎደልን፥ የወደቅን፥ የሞትን ሙታን ነበርን! ጳውሎስ ይህንን በጻፈበት የግሪክ ወሮሜ ባህልና በአዲስ ኪዳን ዘመን ችግረኛ ሕጻናት ብቻ ሳይሆኑ ትልልቅ ሰዎችም ልጆች ተደርገው ይወሰዳሉ። ወሳጁ ሰው ደግሞ ልጆች የሌሉት ወይም ያሉትም ሊሆን ይችላል። ልጆች ከሌሉት ያንን ልጅ አድርጎ የወሰደውን ሰው ወራሹ ሊያደርገው ከመፈለጉ በጎነት የተነሣ ብቻ ነው ልጅ የሚያደርገው። ልጆች ካሉትም አብሮ ወራሽ እንዲሆን፥ የልጆቹ ወንድም እንዲሆን፥ ቸርነቱ እንዲበዛ ሲል ልጁ ያደርገዋል፤ እኩል መብትም ያቀዳጀዋል። ልጁም በስሙ ይጠራል። ይህ የበጎነት ምልክት ነው።
እግዚአብሔር እኛን ልጆቹ ያደረገን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ነው። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። ኤፌ. 1፥5-6።
የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነትስ?
የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ ወደሚለው አሳብ እንምጣ። የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነት ጥቅስ በ2ጴጥ. 1፥4 የሚገኘው ነው። ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። 2ጴጥ. 1፥4
የአማርኛው ትርጉም ገና ሲጀምር በዓለም የሚገኝ ጥፋትን የሚያመጣ ክፉ ምኞትን በመግለጥና ከዚያ ማምለጥን በመናገር ይጀምራል። መለኮት መለኮት መጫወት የሚያምራቸውን ሰዎች ስናይ መጀመሪያ የምናስተውለው ነገር፥ ከዚህ ክፉ ምኞትና ዓለማዊ ጥፋት የራቁ ሳይሆኑ የተጣበቁ መሆናቸውን ነው። ከዓለምና የዓለም ከሆነ ነገር ጋር እየተጫወቱ የመለኮት ባሕርይ ተካፋይነትን ማውራት ይመቻል? አይመችም። ዓለምን እንደ ሙጫ ተጣብቀውባት፥ ስጋዊነትን ተላብሰው፥ ገንዘብን እንደ ውኃ እየተጠሙና እየጠጡ የባሕርይ ልጆች ነን ሲሉ ያስደነግጣል።
የመለኮት ባሕርይ በሚለው ሐረግ ውስጥ፥ ‘መለኮት’ ግልጽ አሳብ ስለሆነ፥ ‘ባሕርይ’ የሚለውን ቃል እንመልከት። መለኮት አምላክነት ነው። አምላክ አንድ ብቻ ነውና እኛ በፍጥረታችን አምላክነት የለንም። ባሕርይ የሚለው ቃል በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ φύσις ፉሲስ ወይም ፊሲስ የሚል ነው። ቃሉ ምን ማለት እንደሆነ በሌሎች የተጠቀሰባቸው ቦታዎች ማየት ተገቢ ነው። ቃሉ በአዲስ ኪዳን ወደ 11 ጊዜያት ተጽፎአል። አራቱ ጥቅሶች ባሕርይ ሲሉ የቀሩት ፍጥረት ይሉታል። ፍጥረት የሚለው ቃልም አሳቡን ይገልጠዋል።
2ጴጥ. 1፥4 ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።
ሮሜ 1፥26-27 ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ ስለምንድር ነው የሚናገረው? ሴቶች ፍጥረታቸውን ወይም ሴትነታቸውን ትተው ከሴትነታቸው ሌላ፥ የሴትነት ባሕርይ ወይም ተፈጥሮ ያልሆነውን ሌላ ለመሆን መሞከራቸውን ነው። ባሕርይ የተባለው የተፈጠሩበት ነገር ወይም ፍጥረታዊ ማንነት ወይም ውስጣዊ ማንነት ነው።
ሮሜ 2፥14 ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ ይህም የሚያሳየው ሰዎች ሰዎች ብቻ ስለሆኑ መለኮታዊውን ተሻጋሪ ሕግ ወይም የሕሊና ሕግ ሊኖሩት ሊታዘዙት በውስጣቸው እንደሚያውቁት ይገልጣል። ይህ ባሕርይ የተሰኘው ነገር የውስጥን ማንነት ገላጭ ቃል ነው። ለምሳሌ፥ አትግደል የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ያልሰማና ያልተማረ ሰው፥ በፍጥረቱ መግደል መጥፎ መሆኑን ያውቃል።
የጸሎት ዋንኛ መለያው ምንድን ነው? ያዥጎደጎድናቸው የተሰካኩ ቃላት ናቸውን? ውብ እና የተመረጡ ቃላት አምላክ በእርግጥም ይገባዋል። ማሳካቱንም ሆነ ማዥጎድጎዱን ከቻልነው እና ከታደልነው እሰየው ነው። ቃላቶቹ ብቻቸውን ግን ጸሎት አይደሉም፤ በጸሎት ውስጥ የሚፈለግ ልብ አለ። ቃላት ያጣንለት መቃተት በፊቱ ያነሰ ዋጋ ይኖረው ይሆንን? አይመስለኝም! ነገር ከቦን በትካዜ ውስጥ ሆነን እህህ ያልናቸው ቃላትስ? ቃላት አጥተን ያነባነው ዕንባ እና ለቅሶዋችንስ? በፊቱ በዝምታ ስንቀመጥስ? እኚህም እንደተሰካኩት ውብ ቅላት ሁሉ በፊቱ እጅግ የከበሩ ናቸው። አብርሀም ኩዩፐር እንደሚል “ነፍሳችን ህያው በሆነ እና ጩኽታችንን በሚሰማ አምላክ ፊት መገኘቷን ተገንዝባ ወደ እርሱ ያሰማችው” ማንኛውም ድምጽ በእርግጥም አምላክ የሚያከብረው እና የሚመልሰው ጸሎት ነው። ወዳጆቼ የጸሎታችን ቅርጽ ሳይገድበን በፊቱ ከጮኽን በእርግጥም አምላክ የሚሰማውን ጸሎት ጸልየናል። እንድንጸልይ አምላክ በጸጋው ያግዘን። አሜን!
ተካልኝ ነጋ (ዶ/ር)
• ከውስጥ ሞልቶ ለትውልድ የፈሰሰ የግል ተሐድሶ •
«ክርስቶስን ካማሳፈር አንድ መቶ ጊዜ መሞት ይሻለኛል» — ጆን ካልቪን
በዓለምና በቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካላቸው ታላላቅ መሪዎች መካከል፣ የፈረንሳዪ ጆን ካልቪን በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው። የሕግ፣ ሥነ-መለኮት፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ጽሁፍ፣ በተለይም ጥንታዊ ግሪክ-ሮማ ሥልጣኔና ቋንቋዎች ጥናት ሊቅ ነበር። በታሪክ ውስጥ፣ በነገረ አስተምህሮ፣ በተለይም በድነት ዙሪያ፣ በቤተ ክርስቲያን ማንነትና ተልእኮ፣ በትምህርት፣ በዲሞክራሲ፣ በመንግሥትና ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መሠርታዊና ሥር-ነቀል የሆነ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በ1533 አካባቢ፣ አንድ ቀን የወንጌል ብርሃን በልቡ ላይ በራ - ሊቋቋመው ያልቻለው ትልቅ ብርሃን! ስለ ልቡ ለውጥ ሲናገር እንዲህ ብሎ ጸፏል፣ “እግዚአብሔር ልቤን በድንገት ለወጠው፤ ለእውነተኛውም የወንጌል ቃል አንበርከከው። በየዕለቱ እየጨመረ በሚሄድና የእግዚአብሔርን ቅድስና በሚጠማ መንፈሳዊ የውስጥ ግለት ነፍሴ ታሰረች።” (John Dillenberger, John Calvin, Selections from His Writings, 26)። ስለዚህ ወንጌል፣ “የንግግር ችሎታ፣ ወይም ከአፍ የማያልፍ ሕይወት የለሽ ደረቅ ታሪካዊ ዶክትሪን ሳይሆን ሥር-ነቀል የሆነ የሕይወት መልእክት ነው። በአእምሮ የግል ጥረት፣ በረቀቀ አመንክዮና ሙት በሆነ ሃይማኖታዊ ግልብ የፊደል ሽምደዳ ሊረዱት አይችሉም። የወንጌልን ጉልበት መረዳት የሚቻለው፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ነፍስንና የውስጥ ልብን ሰርስሮ ሲገባ ብቻ ነው።" በማለት የወንጌልን ከሰው፣ በሰው ያልሆን ፈጹም መለኮታዊነት በሕይወት ምስክርነትና በአስተምህሮ ብቃት ሞግቷል። (Calvin, Golden Booklet of A True Christian Life, 20-21)።
የካልቪን ጥማት የእግዚአብሔር ክብር ነበር። ይኸው በግል ሕይወቱ ሞልቶ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ክብር ነበር፣ የቤተ ክርስቲያንና የዓለምን ታሪክ ዐቅጣጫ ያሰቀየረው። በአደባባይና የግል ሕይወቱ መካካል ምንም የግብዝነት ክፍተት አልነበረም። የ24 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት የፈርንሳይ ንጉሥ፣ ቀዳማዊ ፍራንሲስ፣ በወንጌል አማኞች ላይ ባስነሳው ስደት ምክንያት ትውልድ አገሩን ጥሎ ወደ ጄኔቭ እዲሰደደ አድርጎታል። ቀሪውንም ዘመኑን የጨርሰው እዚያው ጂኔቭ የቤተ ክርስቲያን ታማኝ መጋቢ በመሆን ነበር። አራት መድብሎች ያሉት የካልቪን ኢንስቲቲዩት “Institutes of the Christian Religion” ያለፉት አምስት መቶ ዐመታት የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ቋሚ ቅርስ ነው። (http://www.reformed.org/master/index.html?mainframe=/books/institutes/) ይህን የጻፈው የ27 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት ነበር። ስለጻፈበትም ዋነኛ ምክንያት ሲናገር፣ “ክርስቶስን ለተራበውና ለተጠማው የአገሬ ሕዝብ ካለኝ ሸክም የመነጨ ነው” ብሏል። “በባዚል (ስዊዘርላንድ) ነፍሴን ለማዳን በተደበቅሁበት ሁለት ዓመታት፣ እንደ እኔ ከስደት የማምለጥ ዕድል ያላገኙ የወንጌል አማኝ ወዳጆቼ፣ በሕይወት እያሉ በማገዶ እሳት ጋይተው ስለ ክርስቶስና ስለበራላቸው እውነት ሰማዕት ሆነዋል። ታዲያ ይኽን እያወቅሁ ዝም ብል ከዳተኛ፣ ሰማዕትነታቸውንም አቅላይ ያደርገኛል። የሞቱለትን ጌታና የወንጌሉን መልእክት በፍጹም ንጽህና ለትውልድ ማትረፈ ትንሹ ዕዳዬ ነው። ፈጽሞውኑ ዝናንና ክብርን ፍለጋ አይደለም።”
እኛስ፣ ምን ሠርተን ይሆን የምናልፈው?
የካልቪን የውስጥ ጩኸት፣ በሙት ሃይማኖተኝነት፣ ከቃሉ ጋር በሚጋጭ ትውፊትና በወሰን የለሹ ፍጹማዊ የየጳጳሱ የሥልጣን ቀውስ የተሰወረውን የክርስቶስን ልቀትና ክብር (The supremacy and glory of Christ) ለትውልዱ መግለጥ ነበር። በክርስቶስ የተገኘው፣ የማይቀነስበት፣ የማይጨመርበት፤ ብቁ የሆነ ብቸኛ የድነት ሙሉ ሥራ የካልቪን መካከለኛ አስተምህሮ ነበር። ለካልቪን፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ "ማንም ሊሸፍነው የማይገባ የእዚአብሔር መካከለኛ ግርማ" ነው። በወቅቱ የፓፓው ሥልጣን ከቃሉ በላይ እንደሆነ ተድርጎ ቤተ ክርስቲያን በታወረችበት ወቅት፣ ካልቪን በነፍሱ በመወራረድ፣ “ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ቃሉ ተወለደች እንጂ፣ ቃሉ ከቤተ ክርስቲያን አልተወለደም” በማለት ፊት ለፊት የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ተቃውሞ ነበር። (Institutes, 1.7.2)
ካልቪን በብዙ መከራ ውስጥ እያለፈ ነበር ጌታውንና ትውልዱን ያገለገለው። መዝሙር 124፣ በተለይም፣ ቁጥር ስምንት፣ "ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው።" የልቡ ጥቅስ ነበረች። ባለቤቱ ኢደሌት (Idelette)፣ ታማኝ አገልጋይ ባሏ የሞተባትና የሁለት ልጆች እናት ነበረች። የመጀመሪያ ልጃቸው የሁለት ሳምንት ሕፃን ሳለ ሞቶባቸዋል። ስለ ልብ ስብራቱም እንዲህ በሎ ጽፏል፣ “ጌታ በሐዘን ጅራፍ ልቤን ያቆሰለው እስኪመስለኝ ድረስ የልጄ ሞት አጥንቴ ውስጥ ዘልቆ ገብቷል። ይሁን እንጂ እርሱ ራሱ ሰማያዊ አባት ስለሆነ ልጅ ማጣት ምን ማለት እንደሆነ ይገባዋል፤ የእርሱም ፈቃድ ፍጹም፣ ለህጻናትም የተሻለውን ያውቃል በማለት በፍጹም ሉዓላዊነቱ ተጽናናሁ” (T. H. L. Parker, Portrait of Calvin, 71)። በተከታታይ የወለዷቸው ልጆች፣ በመጨረሻም ኢደሌት ራሷ በወረርሽኝ ወይንም በሳንባ ነቀርሳ ምክንያት በተጋቡ በዘጠነኛው ዐመት ላይ ሞታበታለች። በዚህ ሁሉ የልብ ስብራት ውስጥ፣ ልቡን በእግዚአብሔር አምላኩ ያበረታ የተሃድሶ መሪ ነበር፤ ትጉህ፣ የማያሳፍርም ሠራተኛ! በሁለት ሳምንት ውስጥ 10 ጊዜ (እሁድ ቀን ብቻ ሁለት ጊዜ) እንዲሁም በሳምንት ሦስት ቀን ሥነ-መለኮት ያስተምር ነበር። ከዮሐንስ ራእይ በስተቀር በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት፤ በአምስቱም ኦሪቶች፣ በመዝሙረ ዳዊት፣ በኢሳይያስና መጽሐፈ ኢያሱ ላይ ማብራሪያ (commentaries) ጽፏል። ይህን ሁሉ ይባትል የነበረው፣ በጄኔቭ የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን መጋቢነቱ በተጨማሪ ነበር። በየቤቱ የታመሙትን፣ የተቸገሩትን፣ የተጨነቁትን፣ ወላጅ አልባዎችንና ችግረኛ ባልቴቶችን በታማኝነት ይጎበኝ ነበር። መጋቢነት በተግባር ማለት ይኸው አይደል? በተገኘበት ማንም ሰው እንዲገድለው ቀዳማዊ ፍራንሲስ ያወጀበት የሞት ዐዋጀ ድባብ በላዪ ላይ እያንዣበበ፣ በቂ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በኩላሊት፣ በጨጓራ ቁስል፣ በሆድ ድርቀትና ተመሳሳይ ጤና መታወክና እንቅልፍ በማጣት ይሰቃይ ነበር። መከራን በትዕግሥት የተቀበለ - ኑሮ ሳይመቸው ያለፈ ታማኝ የወንጌል ባለዐደራ! እንደ ጳውሎስ፣ “በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር። በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤” (2ቆር 1፡ 8-9) ያለባቸው ብዙ ሞትን የተመኘባቸው የጨለማ ወቅቶች አሳልፏል። ይሁን እንጂ፣ “ክርስቶስን ካማሳፈር አንድ መቶ ጊዜ መሞት ይሻለኛል” - I should rather die a hundred times than subject Christ to such foul mockery" ነበር የውስጥ ጥንካሬው! (Henry F. Henderson, Calvin in His Letters, 77.)። እናም፣ ብድራቱን ትኩር አድርጎ ዘላለምን በማሰብ ያገለግለ ባሪያ!
በሁለት ምክንያቶች የአጋቦስ ነቢይነት የብሉይ ኪዳን ነቢያቶች ቅጥያ አለመሆኑን መረዳት እንችላለን። አንደኛ:- አጋቦስ ለጳውሎስ መልእክት ሲያመጣ በብሉይ ኪዳን ነቢያት ዘንድ ልማድ እንደሆነው “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል (thus says the LORD God of hosts)” አላለም። ይህም ቃሉ በአፉ የተቀመጠለት የእግዚአብሔር አፍ የሆነ የሥልጣን ቃል የሚናገር ነቢይ አለመሆኑን ይጠቁማል። አጋቦስ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል ብሎ ትንቢቱን ጨርሶ ዝም አለ። ቀሪውን ለጳውሎስ ውሳኔ የተወ ይመስላል። መንፈስ ቅዱስ እንደ ብሉይ ኪዳኑ መልእክት በነቢያቶቹ አፍ ሊያስቀምጥ የመጣ ሳይሆን አሁን በሁሉም ልብ የታተመ አምላክ በመሆኑ ሁሉም አማኞች ጳውሎስን ጨምሮ የመንፈሱን ድምጽ የመለየት አቅም ነበራቸው ብዙም የሚካበድ አይደለም።
ሁለተኛው ደግሞ ለአጋቦስ ትንቢታዊ መልእክት የጳውሎስ ምላሽ ነቢዩ እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያት አለመሆኑን አመላካች ነው። ዙሪያው ላይ የነበሩ ሰዎች ተደናግጠው ይህ ከይሁዳ አካባቢ የመጣው ሰው የተናገረውን ልብ በል እባክህ ታዘዝ በጎ ምላሽ ስጥ ሊሉት ሲሞክሩ ጳውሎስ የተባለውን ለመታዘዝ እምቢ አለ። ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ያደረጉትን የሌሎችንም ልመና የአጋቦስንም ትንቢት ጳውሎስ ቸል አለ። “እያለቀሳችሁ ልቤን አትስበሩ” ብሎ ወቀሳቸውና ጉዞውን ቀጠለ። ይህ ድርጊቱ አመጽ እንደሆነ ተደርጎ የተጻፈበት ክፍል አናይም። ሉቃስም አልጻፈም ሌሎች የአዲስ ኪዳን ሰዎችም አላሉም። የብሉይ ኪዳን ነቢይ ዓይነት ቢሆን አስቡት ይህ ጥሰት የት እንደሚያደርሰው። አድማጮቹም የአጋቦስን ትንቢት እንደ ምክር ነው ያሰቡት እንጂ የነቢዩን ትንቢት አላሉም። “ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ፦ የጌታ ፈቃድ ይሁን፡ ብለን ዝም አልን።” (ሐዋ. 21:14) አሉ። የአዲስ ኪዳን ትንቢት የምክር ያህል ክብደት አለው።
ድሮ ጴንጤ ተሳዳቢ አልነበረም ያሁኑ ግን ካልገባው አይጠይቅም የሚሰበር ቅስም ያለኝ መስሎት ይሳደባል። 😀 በውስጥ መስመር የቻልኩት ብዙ ነው። አልጨረስኩም አትሳደቡ ለማለት ነው።
ወርቅነህ ኮየራ
አንዳንድ ሰሞነኛ ሃሳቦች...
የሙግቱ መነሻ ሌላ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ ወደ ጎራ ልዩነት ወስዶናል። እንዳለመታደል ሆኖ አብዛኛው ሥልጡንና የሚያንጽ ውይይት አልሆነም። ስሜታዊነትና ፍረጃ ይበዛበታል። ነጥቦቼን ለማንሳት ከዚህም ከዚያም እላለሁ። (ትላንት ቃል በገባሁት መሰረት 😊)
• ኢትዮጵያ ውስጥ ካሪዝማዊ/ጰንጠቈስጤያዊ ንቅናቄ ከመግባቱ አስቀድሞ አንጋፋ ወንጌላውያን ቤተ እምነቶች ነበሩ። ሉተራውያን (መካነ ኢየሱስ)፣ ፕርስበይቴሪያን/ባፕቲስት (ቃለ ሕይወት)፣ ሜኖናይትስ (መሠረተ ክርስቶስ) ወዘተ ይጠቀሳሉ። ቤተ እምነቶቹ ዐዲሱን እንቅስቃሴ ለመቀበል ተቸግረው ነበር። የሚጠበቅ ስለሆነ ብዙ አይገርምም። በሂደት ግን መደበኛና ኢ-መደበኛ ውይይቶች ተደረገው፥ ጉዳዩ ሰክኗል። የስደቱን ጊዜ ተረዳድተው አልፈዋል። የሚለያዩባቸውን ልምምዶች በሰፊ ልብ እየተቀባበሉ እስከዛሬ አብረው ወንጌልን ይሠራሉ። የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትም ካሪዝማዊ ያልሆኑትንም የሆኑትንም የሚያቅፍ ተቋም መኾኑ የዚህ ጥረት ውጤት ይመስለኛል።
• ካሪዝማዊው ንቅናቄ ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተውን አዎንታዊ ፋይዳ በቀላሉ መካድ አይቻልም። “...በዚሁ በኛው ሀገር፣ የካሪዝማዊ ጰንጠቈስጤ ነፋስ ቤተ እምነታዊ ዐጥሮች ሳይገድበው ለአማኞች መታነጽ፣ ለወንጌል እውነት መስፋፋትና ለቅዱሳን ኅብረት መጠናከር አስተዋጽዖ ያበረከተ መሆኑን ማን ይጠራጠራል?...” ብሎ ይጠይቃል መጋቢ ሰሎሞን አበበ ገ/መድኅን¹። ታዋቂው የዐዲስ ኪዳን ምሑሩ ዲ.ኤ.ካርሰንም “...ከተሻለ ጎኑ ሲታይ፥ የካሪዝማዊ ንቅናቄ ለቤተ ክርስቲያን በረከት ሆኗል። ...እጅግ ብዙ በረከቶችን በዚህ አይነት መንገድ ያደረሰውን ንቅናቄና ፍሬዎቹን ከጉድለት ጎኖቹ ብቻ መገምገም ትክክል አይደለም”² ይላሉ። እስማማለሁ!
• ሁለቱም ጎራ (ቆሟልና ቀጥሏል) ተቃራኒ ሙግት ለማስተናገድ ያላቸው ቦታ እየጠበበ ይመስላል። የሰሞኑ እሰጣገባዎች ይኼን ጠቁመዋል። ምልልሶቹ ከስክነት ይልቅ ስሜታዊነት፥ ከማስረጃ ፍረጃ ይቀናቸዋል (ሁሉም እንደዚህ ናቸው ባይባሉም)። የሚሰነዛዘሩት ዱላ የወዳጅነት አይመስልም። አጓጉል ስም መለጣጠፍ ታይቷል። አንዱ “የመንፈስ ቅዱስ ተቃዋሚ”፣ “ከሃዲ” ወዘተ ብሎ ሌላውን ለማጠልሸት ሁለቴ አያስብም። (በካሪዝማዊነት ካባ ሥር አድፍጠው የሚፈጸሙ ግፎች ላይ በዚህ ልክ ቀናዒ ቢኮን የት በደረስን እላለሁ)። ሌላኛውም ርህራሔ አልባ የቃላት ጦርነት ያካሂዳል፤ በጅምላ “አጋንንታዊ ልምምድ” ለማለት ይደፍራል፤ ያፌዛል። ጎበዝ! መንፈስን መመርመርና መለየት እንጂ መጨፍለቅን ምን አመጣው?
• የተሓድሶ ጥሪ በተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፍ ውስጥ የዘመናችን አማኞች ትልቁ ችግር ተብለው ከተለዩት ውስጥ “የጸጋ መራጭነትና አንገዋላይነት” የሚል ይገኝበታል። ሲብራራ... “መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን ከሰጣቸው የአገልግሎት ስጦታዎች መካከል የተወሰኑትን በመምረጥ እንደ ባንዲራ ማውለብለብ ብሎም ጥብቅና መቆም። በተለይም ደግሞ ከስብከትና ከትምህርት አገልግሎት ይልቅ ኅይል ይገለጥባቸዋል ተብሎ ለሚታሰቡት የተለየ ቦታ በመስጠት ሌሎችን ማንገዋለል የመሳሰሉት ይስተዋላሉ። ቀጥተኛ መገለጥና ራእይ ላይ ከፍተኛ አጽንኦት በመስጠት የሕይወትና የአገልግሎት መመሪያ ከሆነው ከቃሉ ውጭ ኑሮን መምራት።”³ ይለዋል። ትክክለኛ ግምገማ ነው።
• ቀኖናው ስለተዘጋ አንዳንድ የጸጋ ስጦታዎች ቈመዋል የሚለው ሙግት ቢገባኝ ብዬ ሞክሬ አውቃለሁ። ጥቅሶችን በአቅምቲ ሳልመረምር አልቀረሁም። በብዙ የማከብራቸውንና የምማርባቸውን የነገረ መለኮት ምሑራንን ሙግት ለማንበብና ለማድመጥ ጥሪያለሁ። ነገር ቶሎ አይዘልቀኝም መሰል አልሆነልኝም (ከሐዋርያነት በስተቀር) 😊። በአገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በነገረ መለኮት ተማሪዎችና በጥቂት አማኞች አከባቢ ቅቡልነትን እያገኘ የመጣ አቋም ነው። አስሚታው ገና ስላልታወቀ፥ ብዙ ለማለት ይከብዳል። በቅን ህሊና ቃሉን ፈትሸው ይኼን አቋም ለያዙ ወገኖች ግን አክብሮት አለኝ! ለመማርም ዝግጁ ነኝ።
• አማኞች ተአምራትንና ድንቆችን ከልክ በላይ ከማሳደድ ይልቅ በቃሉ ለተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ በታማኝነት የመታዘዝ ሕይወት ላይ ማተኮር አለባቸው። በአንጻሩም፣ ለካሪዝማዊ ስጦታዎች [ከሐዋርያነት በስተቀር] ዛሬም ክፍት መሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይመስለኛል። ክፍት የሚኮነው - ልምምዶቹ በሐዋርያት ግልጽ መርኽ እስከተቃኙ፣ ዓላማቸውም ቤተ ክርስቲያንን ማነጽና ክርስቶስን ማላቅ እስከሆኑ ድረስ ብቻና ብቻ ነው! አለዚያ ማንም በጨረታው አይገደድም! “ከመንፈስ ፍሬ የራቀን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አራማጅ መምህራንን መሸሽ ይገባናል”!
• ሁለቱም አቋሞች በጤናማው የወንጌላውያን አማኞች “ሰርክል” ለውይይት ክፍት መሆናቸውስ ለምን ይዘነጋል? እንዲህ በቀላሉ የሚብጠለጠሉና፤ በቀላሉ የሚታረቁም አይደሉም! ምናልባት ጌታ እስኪመጣ ድረስ!
• ቄስ አለሙ ሼጣ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ወንጌውያን ኅብረት ፕሬዝዳንት የነበሩ ሰው ናቸው። የመካነ ኢየሱስን ቤተ ክርስቲያንን አቋም ከካሪዝማዊ እንቅስቃሴ አንጻር ለሚቃኝ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ በሰጡት ምላሽ፥ ዋይን ግሩደምን [አስተማሪያቸው እንደሆነ ይጠቅሳሉ] ዋቢ ጠርተው የመንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ የሚነሱ ሙግቶችን እስከ አምስት ያደርሱታል⁴። ዝርዝሩ የዚህ ጽሑፍ ዐላማ አይደለም። ሙግቱ “ቆሟልና ቀጥሏል” ብቻ አይደለም ለማለት ነው። ቄሱ የአብዛኛው ነባር ወንጌላውያን ቤተ እምነቶች አቋም ከሁለቱም ጎራ በትንሹም ቢሆን ለየት እንደሚል ጠቊመዋል።
Open, but Cautious ይሉታል! (“ክፍት ግን ጠንቃቃ”) እዚህ አከባቢ ነን ለማለት ነው እንግዲህ ሃተታ ያበዛነው። መንፈሳዊ ስጦታን ሳያዳፍኑና ደግሞም ሾላ በድፍኑ ብለው ሳይውጡ - መመርመር የአማኞች የውዴታ ግዴታ ነው የሚል ጎራ ነው 😊
“ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም...በብርቱ ፈልጉ” እንዲል ሐዋርያው... መወጋገዱን ትተን፣ ወደ ቀልባችን ተመልሰን “በእውነት አሳድገን - ጌታ ሆይ በፍቅር...”⁵ ብሎ መዘመሩ የሚያዋጣ አይመስላችሁም? ገንቢ ውይይቶችም በጨዋ ደንብ ከተያዙ ጉንጭ አልፋ አይሆኑም! ጸጋ ይብዛልን 🙏
ዋቢ ጽሑፎች
¹ ሰለሞን አበበ ገ/መድኅን፤ "የደነበረው በቅሎ የአስተምኅሮ ልጓም ይሻል"፣ 2006 ዓ.ም. (ገጽ 76)
² ዲ.ኤ.ካርሰን፤ "መንፈስን ማሳየት- የ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12-14 ሥነ መለኮታዊ ትንታኔ፤ SIM አሳታሚዎች እንደረጎሙት፣ 2008 ዓ.ም (ገጽ 255)
³ የተሐድሶ ጥሪ - መመርመር- መመለስ - መታደስ፣ በመንፈሳዊ ተሐድሶ ፎረም የተዘጋጀ፣ 2009 ዓ.ም.(ገጽ 72)
⁴ Alemu Shetta - A Response to - Tormod Engelsviken: "Gudina Tumsa, the EECMY and the Charismatic Movement" - WDL Publishers, Germany 2010 (Page 192-195)
⁵ የመጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ መዝሙር
ፍጹማን ግርማ
ነቢይነት ቀጥሏል ግን አካሄዱን ቀይሯል።
በበቀደሙ ጽሁፌ በጥቂቱ የክርስቶስን ወደዚች ምድር መምጣት ተከትሎ የብሉይ ኪዳን ትንበያና ተስፋ ፍጻሜን በማግኘቱ… በታደሰው ኪዳን የእግዚአብሔር መንፈስ በሁሉም አማኞች ልብ በመኖሩ፥ … የእግዚአብሔር ቃል ከሙሉ ኃይሉና ሥልጣኑ ጋር በ አማኞች እጅ በመግባቱ፥ …አማኞችም በጸጋው የቀረበላቸውን ድነት ተቀብለው የእግዚአብሔር ልጅነት መብት በማግኘታቸው፥ …. አማኞች ሁሉ ለንጉሡ ካሕናት የመሆን ሹመት ያገኙ በመሆናቸው…እና የጸጋ ሥጦታዎች ለሁሉም አማኞች መንፈስ እንደሚፈቅድ ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ የተሰጠ በመሆኑ … ምክንያት የብሉይ ኪዳን አይነት ቃሉ በአፋቸው የሚገኝ “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል” ባይ ነቢያት ያልቀጠሉ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን የነቢይነት ጸጋ የቀጠለ መሆኑን አንስቼ ነበር። የኔ ጽሁፍ አልቀጠለም ግን ቀጥሏል የሚል ዓይነት ይዘት አለው። ለዚህ ነው ርዕሱን “ነቢይነት ቀጥሏል ግን አካሄዱን ቀይሯል” ያልኩት።
ለመግቢያ ይህንን ያህል ካልኩ ይበቃል። ከታች የምጽፈውን የምጽፍበት መረዳት ምን ገጽታ እንዳለው ልናገር። አሁን ላይ ሆነን ስለ ነቢያትና ስለ ትንቢት ጸጋ ስናወራ ለቤተ ክርስቲያን ስለተሰጠው የአገልግሎት ጸጋ ማለታችን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በአዲስ ኪዳን መነጋገር የሚኖርብን ስለ ግለሰብ ሳይሆን ስለ ሥጦታው ነው። (ሥጦታው ስለሚገለጥበት ግለሰብ ሳይሆን ስለሚገለጠው ጸጋ ስለ ራሱ ነው።) ለምሳሌ ያህል ስለ ፈውስ ሥጦታ የምንነጋገር ቢሆን “ፈዋሽ” እያልን ስለ ግለሰብ አንነጋገርም። ስለ ታምራት ሥጦታ የምናወራም ከሆነ ስለ “ታምረኛ” ሰው አናወራም። ስለ ልሳንና ትርጉም ስናነሳም ስለ ልሳነኞችና ስለ ተርጓሚዎች ማውራታችን አይደለም። ነገሮችን ቶሎ ወደ ግለሰብ የመውሰድና “ለዚህና ለዚያ ነው ይህንን የምትለው” የሚሉት አባዜ ሰልችቶኛል። እስከ ዘር ቆጠራ የሚሄዱም አሉ።
ይህንን ለማሳሰቢያ ያክል ካነሳሁ “የጸጋ ሥጦታዎች በሙላት በቤተ ክርስቲያ ይሠራሉ” ብዬ የማምነው ለምንድነው? የሚለውን የመግቢያ መግቢያ የመጨረሻ መግቢያ አድርጌ ላንሳ። በነገራችን ላይ ስለ ጸጋ ሥጦታዎች አንስተን ስናወራ “ቀጥሏል”… “ቆሟል” ብሎ ነገር የለም። ምክንያቱም የጸጋ ሥጦታዎች ከመንፈሱ መውረድና ከቤተ ክርስቲያን መመሥረት ጋር አብረው የተጀመሩ የአዲስ ኪዳን የቤተ ክርስቲያን ገጸ በረከቶች ናቸው እንጂ ከዚያ ቀደም በሁሉ አማኞች ሕይወትና አገልግሎት ሲሠሩ አልነበረምና “ቀጥሏል”… “አልቀጠለም” የሚያስብል ምንም መነሻ ምክንያት የለም። በብሉይ ኪዳን አማኝ ሁሉ የጸጋ ሥጦታ ተቀባይ ቢሆን ኖሮ ምናልባት እንደ ነቢያቱ ቆሟል ቀጥሏል ማለት ይቻል ነበር። የጸጋ ሥጦታዎች በሙላት አንዱም ራሱን ነጥሎ በበቃኝ ሳይወጣ እየሠሩ ለመሆናቸው በርካታ ምክንያቶችን ማቅረብ ቢቻልም ጥቂቶቹን ላንሳ።
1. ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን አደራ ወይም ኃላፊነት ያለ ጸጋ ሥጦታዎች መፈጸም አትችልም።
የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጸጋ ሥጦታዎች ካስፈለጓት የዛሬ ቤተ ክርስቲያን ይልቅ አብልጦ ያስፈልጋታል። እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካይነት ያኔም ዛሬም ይፈውሳል። ቃሉን ይልካል። በድንቅ በተዓምርም ይሠራል። ዳን ካላለህ ፍንግል ትላለህ። ሐዋርያው ጳውሎስ የተዓምራት ጸጋ በጉባኤው መሥራቱን የገላትያን ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት አስታውሶአቸው ነበር። “እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው?” (ገላ. 3:5) እግዚአብሔር ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈሱንም ይሰጣል በሕዝቡ ላይ ታምራትንም ያደርጋል።
2. የእግዚአብሔር ቃል የጸጋ አሠራር በቤተ ክርስቲያን እስከ ክርስቶስ ዳግም መምጣት ሳይጓደል ቀጣይ መሆኑን ተናግሯል።
“ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደ ጸና፥ በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና። እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤(1ቆሮ. 1:5-7) ይህ ለግለሰብ ሳይሆን ለመላው የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ መልዕክት ነው። ታዲያ በዚህ መሠረት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እርሱ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ምንም የሚጎድላት የጸጋ ሥጦታ አይኖራትም። ሲጀምር ጸጋ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጥ እንጂ ለግለሰብ የሚታደል አይደለም።
3. ፍላጎቱ እስካለ ድረስ መግቦቱ “ቆሟል” ማለት በደል ነው። እግዚአብሔርንም አድሎአዊ ማድረግ ነው።
“ለያኔዎቹ ተሰጥቶ ወይም ሠርቶ ለዛሬዎቹ አቋርጧል” አያስኬድም። በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ጥርጣሬ ባይኖረኝም ለእግዚአብሔር ያኔም ዛሬም በክርስቶስ ደም የተዋጀች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ያለቺው ከመሆኑ አንጻር ነው። እግዚአብሔር ሁሉንም የጸጋ ሥጦታዎች ቤተ ክርስቲያን እንደ አስፈላጊነቱ በሥርዓት እንድትገለገል ሰጥቶአል አይጸጸትም። ሕመም አለ። ፈውስም አለ። ችግር አለ። ከችግር መላቀቅም አለ። ፈተና አለ። መሻገርም አለ። የትኛውም የማምለጫ መንገድ ከእግዚአብሔር ከተሰጠን ጸጋ ነው። ሰው ልኮልንም ሆነ ራሳችንን በራሳችን ረድቶንም ቢሆን እርዳታው ጸጋው ነው። ዛሬም በጸጋው ያንጻል፣ በጸጋው ይሠራል፣ በጸጋው ይቀርጻል፣ ሌላም ሌላም። ያዕቆብ በአምስተኛው ምዕራፍ ከአሥራ አራት ጀምሮ በምዕመናን መካከል የፈውስ ፍላጎት መኖሩንና ጌታም መግቦት እንደሚሰጥ ተናግሯል። ይህም የጸጋ ሥጦታ ነው። በመሪዎች ጸሎት ይገለጣል።
የተነሳሁበትን የነቢይነት “ቀጥሏል ግን አካሄዱን ቀይሯል” የረሳሁ እንዳይመስላችሁ እመለስበታለሁ።
ወርቅነህ ኮየራ
ሰሞኑን መቼም ጉድ ነው።
መጋቢ ዘሌ “የወደፊቱን የሚተነቢይ ነብይ የለም። “አለ” የምትሉ ካላችሁ ስሙን ጥቀሱልኝ” ያለው ጥያቄ ጉድ አፍልቶአል። ቀጥሏሊስቶችና ቆሟሊስቶች በሚል የወንጌል አማኞችን ለሁለት እያደረገ ያለ ይመስላል።
ዘሌ ስማቸውን ጥቀሱ ብሏችሁ እንዲህ ከተንጫጫችሁ እኔ እሱን ትቼ ሌላ ጥያቄ ላቅርብ።
“የወደፊት” ተንባዮች ካሉ ትንቢታቸው ስለ ምን ሊሆን ነው? ከአሥር ቀን በኋላ ቡሃቃህ ይሞላል?፣ ከሁለት ወራት በኋላ ምቹ መኝታ ላይ ትተኛለህ? አሪፍ መኪናና ዘመናዊ ቤት መንገድ ላይ ነው? የቢሮ ጠረጴዛና ወንበር ስትቀይር ይታየኛል? ስለ ሹመት ስለ አሜሪካ ቪዛ? ስለ ኳስ አሸናፊ ቡድኖች?፣ …???
1. የብሉይ ኪዳን ተንባዮች የመጨረሻ ግባቸው ክርስቶስ ነበር። ክርስቶስ ከመጣ ሁለት ሺህ ዓመታት አለፉት አይደል? ስለ ዳግም ምጽዓቱ ነው ከተባለ በቂ መረጃ ክርስቶስ ሰጥቶአል አይደለም? ክርስቲያን ከክርስቶስ መምጣት በላይ ተስፋ አለው? ተንባይ ካለ ምንድነው ስለ ወደፊቱ ሊተነበይ የሚችለው?
2. የብሉይ ኪዳን ነቢያት ኃጢአት ሊያስከትል የሚችለውን ፍርድ ጠቅሰው ያስጠነቅቁ ነበር። አያይዘውም ለሕዝቡ የአኗኗር መርህ ያስተምሩ ነበር። አሁን ያንን ለማድረግ ቃሉ በቂ አይደለም? የሰውን ልጅ የግብረገብ ሥርዓት ወይም የሕይወት መርህ በመናገር ለማስጠንቀቅ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚናገሩት አንሶ ነው? ስለሚመጣው ፍርድ ነቢይ ተነስቶ ካልተነበየ ማወቅ የምንችልበት መንገድ የሌለን ነን?
3. በብሉይ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ገና በአማኞች ውስጥ አይኖርምና እግዚአብሔር በትንቢት ቃል የወደፊቱን እያሳየ ያስጠነቅቅ ነበር። ተስፋ እየሰጠ ያጽናናቸው፣ ይመራቸው፣ ይመክራቸው ነበር። አሁን አማኝ ሁሉ መንፈሱን ተቀብሎ ከአምላኩ ጋር ኅብረቱን አጥብቆ በየቀኑ በጸሎት ይገናኛል አይደል? የወደፊት ተንባይ በውስጣችን አሁን ካለው መንፈስ በምን ተሽሎ ነው? ትንቢቱስ ምን ሊሆን ነው?
ክርስቶስ መጥቷል። ቃሉ ከፍጹም ሥልጣኑ ጋር እጃችን ገብቶአል። መንፈስ ቅዱስ ላይለየን በውስጣችን ታትሞአል ደግሞም ይሞላናል። ኪዳን ታድሶ አሠራር ተለውጦ አማኝ ራሱ ካሕን ሆኗል። አማኞች እርስበርስ እንዲተናነጹና ጌታን በጋራ እንዲያከብሩ ጸጋ ለሁሉም አማኝ በመንፈሱ አማካይነት ተከፋፍሏል። አሁን በዚህ ጊዜ ተንባይ ቢኖር ትንቢቱ ስለ ምን ሊሆን ነው? የወደፊት ተንባይ ካለ ምን ይተነብያል? ነው ጥያቄዬ🤔
የጸጋ ሥጦታዎች ቆመዋል የሚል ሰው አለ ብዬ አላምንም። እኔም እንደሱ ማመን አልችልም። የብሉይ ኪዳኑን ኢዩ እየጠሩ ስማቸውንም ከዘፍኔነት ወደ ኢዩነት ቀይረው “በበቀል ቅባት ተቀብቻለሁ” እያሉ በጴንጤው መካከል ለሚነሱት “ነቢይ ነን” ባዮች ግን ምንም ቦታ የለኝም። ደሞ በምሕረት ዘመን “የበቀል” ነቢይ ውይ። 🙄እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን ዓይነት ነቢያቶች አያስፈልጉትም። በልጁ ከተናገረው፣ በመንፈሱ በውስጣችን ከሚመሰክረው፣ በቃሉ ተጽፎ ከተሰጠን የሚበልጥ ወይም የሚሻል ትንቢትም አይኖረውም። ጌታ አምላክ ዘላለምን ገልጦልናል።
በድንግዝግዝ አንሄድም ብርሃን በርቶልናል። “ምን ይሻለናል” እያልን ለየቀን ጉዳያችን የምናስተነብየው የቤቱን በር እንደ አዞ አፍ ከፍቶ የሚጠብቀን ሰው አያስፈልገንም። አደናጋሪ ነገር የለም። የሚበቃንን ያህል ሰምተናል። የሚበቃንን ያህል አግኝተናል። አሁን ሰው መጥቶ “ተንባይህ ነኝ” ብሎ ቢነግረን ባይነግረንም ግዴለንም። ረክተናል ተረጋግተናል። ወዴት እንደምንሄድ እንዴት እንደምንሄድ አውቀናል። “ከአፌ ቃል በቀር” እያለ ትኩረታችንን የሚስብ እግዚአብሔር በ አፉ ቃል የሚያኖርለት ሰው ያኔ እንደነበረው አሁን የለም። ቃል አልባ ቃል አውጪዎችን አንሰማም።
ደመና ሊከድነው በማይችል መልኩ ክብሩን አይተናል። ጸጋውን ተቀብለናል። በክርስቶስ ያልሰማነው መልዕክት የለም። በርሱ ያልተቀበልነው ሥጦታ የለም። በርሱ ያልተባረክነው በረከትም የለም። የብሉይ ኪዳን የወደፊት ትንቢቶች ክርስቶስን ያመለክቱ ነበር። ለሕዝቡ ቀጣይ ምሪት ይሰጡ ነበር። የመንፈሱን መምጣት ተስፋ ይሰጡ ነበር። ግብረገብን አኗኗርን ያስተምሩ ያስጠነቅቁ ነበር። አሁን ይህ ሁሉ አስፈላጊ አይደለም። ከኪዳኑ መታደስ ጋር ክርስቶስን ስንቀበል ሁሉ በርሱ አንዴ በጃችን ገብቶአል።
የጸጋ ሥጦታዎች ቀጥለዋል ቆመዋል የሚለውን ግን ከዚህ ሓሳብ ጋር የሚያይዘው የለም። “የወደፊት ተንባዮች አሉ ወይ?” ለሚለው “አሉ!” ወይም “የሉም!” ማለት ነው እንጂ ሌላ ድንጋይ ማንሳት ምንም አይጠቅምም። እኔ በበኩሌ የጸጋ ሥጦታዎች ሁሉም ቀጥለዋል ብዬ አምናለሁ ። ለምን እንደማምን ሌላ ጊዜ በሥፍራው አብራራለሁ። በዚህ ዘመን አሠራሩ ሲለይ አካሄዱ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሲሆን ማየታችን ሥጦታው “ቆሟል” ለማለት ምንም መነሻ አይሆነንም። ፌክ የብር ኖት መኖሩ እውነተኛው ከአገር ጠፍቶአል አያስብልም። ትንቢትም፣ ትምህርትም፣ ልሳንም፣ ፈውስም አሉ። አጠቃቀሙና ዓላማው መቃወሱ እውነት ቢሆንም ሕክምና ያስፈልገዋል እንጂ “ቆሟል”ን ምን አመጣው?
ወርቅነህ ኮየራ
ኀጢአት በእግዚአብሔር ላይ ቀጥታ የተሰነዘረ ዐመፅ ነው። በኀጢአት ምክንያት፣ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ክብር ጐድሎታል፤ ጦሱም በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቁጣና የሞት ፍርድ ሥር አስቀምጦታል። በኀጢአት ምክንያት፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድና ሁለት የነበረ የፍጥረት ስምረት፣ እግዚአብሔር ብቻ እንዲሁ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊያስታካክለው በማይችል ሁኔታ ተቃውሷል።
ኀጢአት የእግዚአብሔርን ክብር ከሰው ላይ ግፍፏል። (ሮሜ 3፥23፤ 5:12፤ ኤፌ. 2፥1)። የሰው ልጅ ቀዳሚ ችግር ከፈጣሪው እግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት መሰበር ነው። በተሰነጣጠቀ መስታወት ውስጥ የሚታይ ምስል ጥፉ (disfigured) እንደሚሆን ሁሉ፣ አምሳለ እግዚአብሔር (Imago Dei) የሆነው ሰውም ጥፉ ሆኗል። ኀጢአት ሰውን ከእግዚአብሔር፣ ሰውን ከራሱ ጋር፣ ሰውን ከሰው ጋር፣ ሰውን ከፍጥረት ጋር ያለውን ግኙነት ሰብሯል፤ ለያይቷል። ከውደቀት በኋላ፣ እግዚአብሔር አዳምን “የት ነህ?” ብሎ ሲጠይቀው “የቦታ ወይም የአድራሻ ጥያቄ አልነበረም”። ይልቁንም፣ በኀጢአት ምክንያት በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ክብር ማጣቱን እንዲሁም ራሱን ያገኘበትን የውርደት ቦታ እንዲያስብ ነው።
የዓለማችን መሠረታዊ ችግር፣ አገራችንን ጨመሮ፣ ኀጢአት መሆኑንን በማወቀም ሆነ ባለማወቅ የሚክድ፣ የሚያሳንስ፣ ወይም የሚሸፍን ሌላ ምርመራ (diagnosis) ሐሰት ነው። ከዚህ ነባራዊ እውነት ውጭ፣ ለሰው ልጅ “በችግርነትም”፤ በመፍትሔነትም” የሚቀርብለት ማንኛውም አማራጭ፣ የሐሰት ድነት (false redemption) ነው። ሰው ራሱን ማዳን በማይችልበት ሁኔታ “ውዱቅ (fallen)” ሆኗል። የፍጥረትም ስምረት ተቃውሷል። ማኅበራዊም ሆነ ፓለቲካዊ ቀውሶቻችን የሚቀዱት ከዚህ በኀጢአት ከተበከለ ማንነት ውስጥ ነው። የእግዚአብሔር ተልዕኮ፣ ራሱን በአዳኝነትና በፍጥረት አዳሽነት መግለጡ ዋናውና ብቸኛ ምክንያት ሰውን ከኀጢአትና የጦሱ እስራት ለመዋጀት ነው።
ከዘፍጥረት ሦስት እስከ ራእይ ዮሐንስ የምንመለከተው ይህንኑ የእግዚአብሔር የተልዕኮ እንቅስቃሴ ነው። በድነት ታሪክ ውቅር ውስጥ፣ ሰው በኀጢአት ምክንያት ለገባበት ቀውስ በመፍትሔነት እግዚአብሔር ራሱን ገልጧል። አምላክ ሥጋ ኾነ! "ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን።" (ዮሐንስ 1፥14)። ለማክበር እየተዘጋጀን ያለው የልደት በዓል ይህንኑ በድነት ታሪክ ውስጥ ራስና መደምደሚያ የሆነ ዘላለማዊ እውነት ነው፦ “ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” (ገላትያ 4:4)።
የአዳምና የሔዋን ራቁትነት የተሸፈነበት ቆዳ የተገኘው እግዚአብሔር ባዘጋጀው የንጹሕ እንስሳ መስዋዕት ነበር። ልክ እንዲሁ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም የሰው ነውር ለአንዴና ለዘላለም ተሽፈነ! በርግጥ፣ "ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው።"(ቲቶ 3፥5)። ለዚህ እንዲሁ ለተቀበልነው መዳን፣ ራሳችንን ለጌታ ሙሉ ለሙሉ በእውነተኛ ምስጋና ከመስጠት በስተቀር ምን ይመጥነዋል? በክርስቶስ ቤዛዊ የመስቀል ሞት ከእግዚአብሔር ጋርና እርስ በእርስ የታረቀ ማኅብረ ሰብ ብቸኛ መልዕክቱ፣ ኢየሱስ አዳኝና ጌታ መሆኑን ነው። በኑሮአችን፣ በአምልኮአችንና በመልእክታችን የምንስብከው የተሰቀለው፣ የተነሣውና በክብር የሚመለሰው ንጉሡ ኢየሱስ ብቻ ይሁንልን! የተሐድሶ ናፍቆታችንም፣ ይኸው የክርስቶስ ዝና መሰማቱ ይሁንልን።
አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
በኢትዮጵያ የምትኖር ጸረ ሙስና ኮሚቴ ሆይ . . .
ከዚህ ቀደም የጸረ-ሙስና ኮሚሽን የሚባል ተመሥርቶ ነበር። ወደ ዓመት ወይም ካልበለጠ የማያንስ ዕድሜ ኖሯል። ምን እንደሠራ ምን ተግዳሮት እንደገጠመው፥ እምን ላይ እንደከሸፈ አልተነገረም። ብዙ ሥራዎች ሠርቷል ይባላል። እውነት አድርገውት ከሆነ፥ የባለ ሥልጣናት ንብረት ሁሉ ሳይቀር ተመዝግቧል፤ ብዙ ሰነዶችም አስረክቧል ተብሏል። ብቻ ሟሟ። አሁን ጸረ ሙስና ኮሚቴ በይፋ ተመሥርቷል። ኮሚቴና ኮሚሽን ልዩነታቸው በወግ አልታወቀኝም።
ከጸረ ሙስና ኮሚሽኑ ምሥረታ በኋላ ሙሰኞች ደንገጥም ያሉ አይመስልም። እንዲያውም አንዱ ሌላውን እንዳያጋልጥ ይመስላል በማኅበር ተደራጁ። እውነትም በጠቅላዩ የተባለው ቀይ መስመር ቀይ ምንጣፍ ሆነላቸው። የሙስና ቀይ ምንጣፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ተነጥፎ የሚራመዱበት ሳይሆን የሚንጎማለሉበት ሆኗል።
ሙስና የግዕዝ ቃል ነው። በአማርኛ ‘ስ’ ጠበቅ እናድርጋት እንጂ አትጠብቅም። ቀጥታ ትርጉሙ ብልሽት፥ መበስበስ፥ መብከት ነው። ለምሳሌ በሐዋ. 2፥27 እና 31 መበስበስ የሚለው በግዕዙ ይህ ቃል ነው። ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሚለው፥ ‘ወኢትሁቦ ለጻድቅከ ይርአይ ሙስና።’ ይለዋል።
በቤተ ክርስቲያን ያለው መበስበስ ወይም መብከት ወይም ሙስና በሌሎች ቦታዎች እንዳለው የገንዘብ ብቻ አይደለም። የባሰ ነው። ጥቂቶች ፊሽካ ነፍተዋል፤ ጥቂቶች ጮኸዋል፤ ሰሚ የለም። እዚህ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን አካል እየተጎዳ ነው። አካል ውስጥ ነፍስ አለ፥ መንፈስ አለ፥ ክርስትና መንፈሳዊ ሕይወት ነው። ጉዳቱ አካላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ነው፤ አእምሯዊና ስሜታዊ፥ ስነ ልቡናዊና ሕሊናዊም ነው። ጎጂዎቹ የታወቁና ብዙዎቹ፥ ‘ነቢይ’ እና ‘ሐዋርያ’ የሚል ማዕረግ ከስማቸው በፊት የተጻፈላቸውሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ ሐዋርያት ናቸው። ሌላው የጎጂነታቸው ገጽታ እነርሱ ራሳቸው የምስኪኖችን መቀነትና የስስታሞችን ቦርሳ እየበዘበዙ እግዚአብሔርን ተጠያቂ ማድረጋቸው ነው። እግዚአብሔርን ጉቦኛና አሻጥረኛ አስመሰሉት።
በኢትዮጵያ የምትኖር ጸረ ሙስና ኮሚቴ ሆይ . . .
ጉዳዩ የታወቁ ሙሰኞችን ስለ መጠቆም ነው።
ምንም እንኳ እነዚህ ሙሰኞች የኢወአአ/ክካ (ቆንስላው) አባላትና መሥራቾች፥ አንዳንዶቹም አዋላጆች ቢሆኑም፥
ምንም እንኳ ይህ ቆንስላ ራሱ የተወለደው፥ የተበጀው፥ ሥጋና ደም የለበሰው፥ የሕይወት እስትንፋስም እፍ የተባለበት በቤተ መንግሥት ቢሆንም፥ እነዚህ አስቀድሞም የተረጋገጠላቸው በተከታዮቻቸው የተጨበጨበላቸው ሙሰኞች ናቸውና ስለ ማዋለጃው ቦታ ብቻ ተብሎ ሙሰኝነት ፈቃድ እንደማይሰጠው ተስፋ አደርጋለሁ። አንዳንዶቹ ይህንን የቆንስላ መታወቂያቸውን እንደ diplomatic immunity እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። አንዱ ሐሰተኛ ይኸው የቆንስላውን መሪዎች ይዞ በደቡብ አፍሪቃ እከከኝ ልከክህ እየተባባሉ ይገኛሉ። ብቻ ስለ ማዋላጀው ቦታ ተብሎ ራሱ ቆንስላውም ተዝቆ የማያልቅ ዐዛባ ነውና እሱም ባይታለፍ መልካም ነው እላለሁ።
ጸረ ሙስና ኮሚቴ ሆይ . . .
ይህ የሃይማኖት ጉዳይ መሆኑ ይታወቀኛል። ‘መንግሥት በሃይማኖት፥ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም።’ በሚለው አንቀጽ 11 መሸነጋገል እንዳንችል፥ አንቀጽ 27/5 ደግሞ ጉዳቶች ሲከሰቱ መንግሥት ጣልቃ እንደሚገባ ወይም እገዳ ሊኖር እንደሚችል በጥቁርና ነጭ ተጽፎ ይታያል። ይህ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ እንዲጠበቅና ጸረ ሙስና ኮሚቴው ይህንንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቀይ ምንጣፍ ላይ የሚጓደዱ ሙሰኞች እንዲፈትሽ ብጠይቅ ይህ ብዙ መጠየቅ አይመስለኝም።
ዘላለም ነኝ።
ከእርሱ ከራሱ፣ በራሱ፣ ኅልው ከሆነው በቀር ሁላችንም ጥገኞች ነን! "ራስ መቻል" የመግባቢያ ቋንቋ ነው እንጂ "ራሱን የቻለ" እንድ ብቻ ነው!
እግዚአብሔር ኢ-ጥገኛ፣ ነፃ ፣ በራሱ ኅልው ነው።
ማንም በማይጋራውና ለእርሱ ብቻ በሆነ መልኩ ሰልፍ ኤግዚስተንት/በራሱ ኅልው ነው! ይህ ከማንም ምንም ሳይፈልግ መኖሩ፣ በሌላ በማንምና በምንም ዘንድ አይገኝም። ለእርሱ ኅልውና ሲጀምርም ሰበብ የሆነው፣ ሲቀጥልም ምግብ የሆነው ምንምና ማንም የለም! ለመኖሩም ማናችንም አናስፈልገውም። በሰማይም በምድርም፣ ሌሎች ነገሮች ሲፈርሱ፣ ሲሰነጣጠቁ ከኅልውናው ጋር አይነካኩም፣ ራሳቸውን ችለው ‘ረብ! ይላሉ። ስለዚህ የትክክል መለኪያ እርሱ ብቻ ነው ማለት ነው!
እግዚአብሔር ኢ-ጥገኛ፣ ነፃ፣ በራሱም ኅልው ነው ስንል፣ በምግባሩም፣ በሕጉና በሥራው ሁሉ ነፃና ራሱ ለራሱ የበቃ ነው ማለታችን ነው። (የሐዋ 17፡ 24-25)
“ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። “
ስለዚህ፦ አንድ ነገር ውጤት የሚሆነው ሳቢያ ሲኖረው ነው፣ ውጤት ያላስከተለ ማንኛውም ነገር ሳቢያ አይሆንም፣ እግዚአብሔር ውጤት አይደለም፣ እርሱ ግን የሁሉም ውጤቶች ሰበብ ነው። በዚህ ማንነቱ ነው ለሙሴ የተገለጠው “ያለ፣ የነበረና የሚኖር” ለእርሱ አንባሪ፣ አኑዋሪ፣ የማያስፈልገው።
እግዚአብሔር “የማይችለው” ነገር ቢኖር “አለመኖር” ነው፣ አንድ ነገር ዘላለማዊ የሚሆነውም፣ አለመኖር ስለማይችል ነው - ሌሎች ግን መኖር አልቻሉም ያልፋሉ። እግዚአብሔር ገና ከመጀመሪያው ኅልው ነው፣ ያልነበረበት ጊዜም አልነበረም!
“እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤ እግዚአብሔር ኃይልን ለበሰ፥ ታጠቀም፤ ዓለምን እንዳትናወጥ አጸናት። 2 ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀ ነው፥ አንተም ከዘላለም ነህ። 3 አቤቱ፥ ወንዞች ከፍ ከፍ አደረጉ፥ ወንዞች ቃሎቻቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ። 4 ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው። 5 ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው፤ አቤቱ፥ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል።” መዝ 93:1-5
ስለዚህ፦ ዙፋኑ እድሜው ስንት ነው አይባልም! ጊዜ ሳይኖር ነበር፣ ከጊዜ ውጪ የነበረው ነው በጊዜ ውስጥ ወዳለነው በሥጋ የተገለጠው፣ ሁሉ ነገር ያለው አንድ ነገር ስለነበረ ነው እርሱ ግን ያለው ምንም ነገር ስለነበረ አይደለም “before me there was no God formed, neither shall there be after me” (Isa 43:10-11)
“ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም። ገልጫለሁ፤ አድኛለሁ፤ ተናግሬአለሁ፤ በመካከላችሁ እኔ እንጂ ባዕድ አምላክ አልነበረም። እኔ አምላክ እንደሆንሁ፣ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከጥንት ጀምሮ እኔው ነኝ፤ ከእጄም ማውጣት የሚችል የለም፤ እኔ የምሠራውን ማን ማገድ ይችላል? ስለዚህ እንመነው
እርሱ የሚያከብረው ሌሎች ያወጡት ሕግ የለም! እርሱ በአጥናፈ ዓለሙ ውስጥ ያሉትን የመኖር ሕጎች በሙሉ ሠርቷቸዋል፣ እርሱን ግን የሚገዛውም ሕግ የለም፣ እርሱ በሉዓላዊነቱ የመንቀሳቀሻ ሕግ ያወጣል፣ ለራሱ ግን ሕጉ ራሱ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በሕግ አምላክ አይባልም፣ ይልቅ“ስለ ስምህ ስትል” ተብሎ ይጠየቃል።
ስለዚህ፦ ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ተአምራት ለሰው ልጆች ጥቅም፣ ለጌታም ክብር የሚፈጸሙት ሕጋቸውን ባወጣው፣ ሕጋቸው ተጥሶ ነው፣ አጭሩ ቢረዝም፣ ባዶው ቢሞላ፣ ዐይነ ስውር ቢያይ፣ የማይሰማ ቢሰማ፣ ሕጉን ያወጣው በሕጉ ውስጥ ጣልቃ መግባትና የማድረግ አቅምና መብት ስላለው ነው።
መጋቢ ሰሎሞን ጥላሁን
ወንጌሉ ስለ እርሱ ነው፤ ወንጌሉ የእርሱ ነው።
የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ። ማር. 1፥1
ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። ሐዋ. 8፥35
ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ። ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሮሜ. 1፥1-4
በልጁ ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና፤ ሮሜ 1፥9
ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ፤ ሰብኬአለሁ። ሮሜ 15፥19
ነገር ግን የክርስቶስን ወንጌል እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ በዚህ መብት አልተጠቀምንም። 1ቆሮ. 9፥12ለ
ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይሆንን? 2ቆሮ. 11፥7
በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። ገላ. 1፥6-8
ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። ፊል. 1፥27ለ
ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? 1ጴጥ. 4፥17
ወንጌሉ ስለ እርሱ ነው፤ ወንጌሉ የእርሱ ነው።
አንሸቃቅጠው።
ዘላለም ነኝ።
"መዳን ከእኛ ውጪ ነው ብሎ ማመን አስገራሚ ዜና ዓይደለምን?"
ወንጌላዊው ክርስትና ከሌሎች "ክርስትናዎች" በእጅጉ የሚለየው ጽድቅ በእምነት የምንቀበለው የእግዚአብሔር ጸጋ ለመሆኑ አጽንኦት በመስጠቱ ነው። ድኅነት "በጸጋ ብቻ"፣ "በእምነት ብቻ" የሚባለውም ለዚያ ነው። በእርግጥም ደግሞ ክርስቶስን ማወቅና በእርሱ ማመን የሰው ጥረት ውጤት ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሚገኝ መለኮታዊ መገለጥ ነው። ቃሉን ሰምተን፤ መንፈሱን አግኝተን "እርሱ አምላኬ ነው በራልኝም!" የምንልበት የአብርሆት ቀን እስኪመጣ ነገር ሁሉ ድፍንፍን ያለ መሆኑንም ያለፉበት ያውቁታል።
ወንጌላዊውን ክርስትና ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለየው ሌላኛው መታወቂያም "እምነት እንጂ ሥራ አያጸድቅም" በሚለው እወጃው ነው። መልካም ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሆኑ ቢታመንበትም ለጽድቅ ያግዛል ተብሎ ግን አይታሰብም። ወንጌላውያኑ አማኞች ፤ "ጽድቅ ከእኛ ውጪ ባለ ሌላ አካል (በክርስቶስ) ተሠርቶ አልቆ በጸጋ ገንዘባችን የምናደርገው፣ በእምነት የምንቀበለው የእግዚአብሔር ውድ ስጦታ እንጂ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንደሚሉት እግዚአብሔር በልጁ በሠራው የድኅነት ሥራ ላይ የእኛ መልካም ምግባር ተጨምሮ ምሉዕ የሚሆን ዓይደለም" ባዮች ናቸው።
በእርግጥም ደግሞ፣ ጽድቁ የእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔር ከሆነ በእኛ ተጨማሪ ሥራ የምናሳካው ፣በጾምና በጸሎት ብዛት የምናሻሽለው ፣ በሂደት የምናዳብረው፣ በጊዜ ውስጥ አጎልብተን ወደ ፍጽምና የምናደርሰው ሰው ሰራሽ ጽድቅ አይኖርም። ጾምና ጸሎት ግን በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። "ትቀደሱ ዘንድ ፈልጉ" የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ ማክበርና ራስ ወደሆነው ክርስቶስ ማደግ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ መልካም ፍሬ፣ ደግሞም የፍቅርና የልጅነት ግዴታ ቢሆንም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባው ግን ዕድገት ተለክቶና የቅድስና መጠን ታይቶ ዓይደለም። ነገሩ እንዲያ ቢሆንማ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ!
እነሆ በወንጌላውያኑ እምነት የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ አንድያ ልጁ በቀራኒዮ መስቀል ላይ "ተፈጸመ!" ባለ ሰዓት ፍጻሜውን አግኝቷል። ሥራው ጎልጎታ ጉብታ ላይ ተጠናቅቋል። በዚያ ላይ የሚጨመር ምንም ስለሌለም የዘላለምን ሕይወት የወረስነውና የምንወርሰው ገና ኃጢያተኞች ሳለን በተሠራልን ሥራ እንደሆነ መቁጠር ይቻላል። መጽሐፍም፣"ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጧል" ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ይህ ጸጋ ኃጢያተኛውን ያለ ሥራ የሚያጸድቅ ስለመሆኑ ያወሳል። " ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና" ብሎ ይነግረናል።
በዚህ ላይ ከእኛ ውስጥ አፍልቀን የምንጨምረው፣ ይኼ ጎድሏል ብለን የምናሟላው አንዳችም የጽድቅ ሥራ የለም። የዛሬ 500 ዓመት ግድም ውስጡን ባላሳረፈው የጽድቅ ጥማት ሲሰቃይ የነበረውን መነኩሴና የሥነ መለኮት ኘሮፌሰር፣ ማርቲን ሉተርን ያስፈነደቀውም መዳን ከእኛ ውጪ ተሠርቶ ያለቀ መሆኑን መገንዘቡ ነበር። የዚህ ጽሑፌ ርዕስ ያደረግሁትም ይህንኑ የሉተር አባባል ነው። ይኼ እውነት ለገባቸውም የዜናው አስገራሚነት ሁሌም በልባቸው ይኖራል።
© ሽመልስ ይፍሩ
ተሐድሶው ሲታወስን በቀጥ በዚህ መከታተል ይቻላል
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1179565812636691&id=100000129673109
"ጥያቄ — የተሓድሶ ጅማሬ!"
የፕሮቴስታንት ተሓድሶ (___the Reformation) የጀመረበት መካከለኛው ዘመን (the Medieval Period) ስለ እምነታቸው ብዙ የማያውቁና የማይጠይቁ ምዕመናን የሞሉበት ነበር። ምክንያቱም የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብና ተደራሽነት በውስን የቤተ ክህነት ሰዎች አከባቢ ብቻ የታጠረ ነበር። የሰው ትውፊት፥ ሥርዓቶችና ልማዶች ከቅዱሳት መጽሓፍት በላይ ቅቡል ናቸው። የፖፑ ስልጣን ገደብ አልፎ የመንግስተ ሰማይ መግቢያና የኅጢአት ይቅርታ ሰነድ ሽያጭ (indulgence) ድረስ ተደርሷል።
በብዙ መንፈሳዊና ሞራላዊ ዝቅጠት ውስጥ ለተዘፈቀቺው ለጊዜዋ ቤተ ክርስቲያን፥ በእግዚአብሔር አነሳሽነትና በጀርመናዊው መነኩሴ ማርቲን ሉተር ፈር ቀዳጅነት የተለኮሰው የተሓድሶው እሳት በጥያቄ ነበር የጀመረው። "የወደቀው የሰው ልጅ በቅዱሱ እግዚአብሔር ፊት እንዴት ሊጸድቅ ይችላል?" የሚል ዕረፍት የሚነሣ ጥያቄ!
አዎ! ተሓድሶ ጠያቂ ነው። ለምዕመናን ስለ እምነታቸው ያልገባቸውን ነገር የመጠየቅን ነጻነት ይቸራል። የተነገረውን ሁሉ እንደወረደ እንዳያምኑ፥ በቅን መንፈስ እንዲመረምሩ ይገፋፋል። "አሜን" ከማለት በፊት "ምን? ለምን? እንዴት?" ብሎ የማሰብን ፋታና የመመርመርን መብት ያጎናጸፋል።
ተሓድሶ የሚጠይቀው የጥያቄ ሱስ ስላለበት አይደለም። ወይም አበጥሮ አሳቢ (critical thinker) ወይም ፈላስፋ ለመባል አይደለም። የጥያቄው መነሾ ለእውነት ያለው ጥልቅ መሻት ነው። እንዲሁ ነፋስ እንደመጎሰም ያለ በቂ መመዘኛም/ስታንዳርድ/ አይጠይቅም። እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለባቸውን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደ ቱምቢና ዋቢ ይጠራል። የመንፈስ ቅዱስን የቅዱሳት መጻሐፍት ደራሲነትና ወደ እውነት የመምራት ችሎታ ዕውቅና ይሰጣል።
እንደ ቤሪያ ሰዎች "ነገሩ እንደዚህ ይሆንን?" ብሎ መጻሕፍትን ማገላበጥ የተሓድሶ መለያ ባህሪ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስንም ቢሆን ከመጠየቅ አይቦዝንም። "ጠያቂ አዕምሮን የፈጠረው እግዚአብሔር ሰዎች ያልተረዱትን ሲጠይቁ እንዳለመታዘዝ አይቆጥርም" የሚል መርህ ይገዛል። ተሓድሶው "ቤተ ክርስቲያን ያለቺው፣ ፖፑ/ካህናት ያዘዙን" የሚሉትን አባባሎች "መጽሐፍስ ምን አለ?" በሚል ጥያቄ ተክቷል።
ዛሬ ዛሬ ቁና ሙሉ እንቶ ፈንቶ እየሰበኩ "አሜን" ካላላችሁ በረከቱ ያመልጣችኋል ብሎ ማስፈራራት ተለምዷል። በጨፈኑ ቁጥር በትንቢትና "ታየኝ" ስም ግልጽ የሆነውን የቃሉን እውነት የሚጋርዱ በዝተዋል። እነዚህ የቃሉና የተሓድሶ ጠላቶች ናቸው። ተሓድሶው እምነትና ድነት በጅምላ፣ በውክልናና በጭፍን መሆኑን አስቀርቷል!
ለዚህም ነው ተሓድሶው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያልነበረን ዐዲስ ነገር አላመጣም የሚባለው። ይልቁንስ፥ ከቅዱሳት መጻሕፍት ላይ አቧራውን አራገፈ፤ በእውነት ላይ ባጠላው ጭጋግ የቃሉን ብርሃን ፈነጠቀ። በቤተ ክህነት ሰዎች የረከሰውን አትሮኖስ ለቃሉ ፍጹም ሥልጣን በማስገዛት ቀደሰ! ባጭሩ "ተሓድሶው" ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቀደመው አምልኮተ-እግዚአብሔርና የወንጌል ተልዕኮ ለመመለስ ይጠይቃል!
የተሓድሶው ሲታወስ መርኅ ግብር ዓላማም ይኼ ነው። ከየት እንደወደቅን ዙሪያችንን በመቃኘት "እንዴትና ለምን?" ብሎ መጠየቅን ማበረታት፤ የዘመናችንን ወንጌላዊ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ካቈጠቈጡና ማንነቷንና ግብሯን ካደበዘዙባት ዕድፋም አስተምህሮዎችና ባዕድ ልምምዶች ነቅታ ውስጧን እንድትፈትሽ ማንቃት፤ እንድትጠይቅ ማስቻል ነው። እውነትን የሚጠማ ጥያቄ ባለበት በዚያ እግዚአብሔራዊ ተሓድሶ መሰረት ይጥላል! ልከኛ ጥያቄም እውነተኛ ተሓድሶን ይቀድማል!
የቅዳሜና ዕሑድ ቀጠሯችን እንዳይረሳ!
ሣር ቤት ሙሉ ወንጌል — ከ9፡00 ሰዓት ጀምሮ👇
ፍጹማን ግርማ
ገላ. 4፥8 ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ ገላ. 4፥8 በባሕርይ አምላክ አለመሆን ግልጽ ነው። ምንም አምላክ የለም፤ ከአንዱ በቀር። አምላክ ተደርጎ የሚመለክ የለም ማለት አይደለም። ግን ያ ጣዖት እንጂ አምላክ አይደለም። ወይም መለኮት አይደለም። እነዚህ ጣዖታት ፍጥረቶች፥ ፍጡራን፥ ወይም አጋንንት፥ ወይም የሰው እጅ ሥራ የሆኑ ቅርጻ ቅርጽ ናቸው እንጂ አምላክ ወይም መለኮት አይደሉም። በባሕርያቸው፥ በማንነታቸው ወይም በምንነታቸው አማልክት አይደሉም። ውስጣዊ፥ የራሳቸው የሆነ፥ ፍጥረታቸው የሆነ፥ አምላክነት የላቸውም።
ይህ φύσις የተባለው ቃል ከላይ ባየናቸው ጥቅሶች ውስጥ ባሕርይ ተብሎ ሲተረጎም ወይም ሲሰኝ በተቀሩት ቃሉ በተጠቀሰባቸው ጥቅሶች በሮሜ 2፥27፤ 11፥21 እና 24፤ 1ቆሮ. 11፥14፤ ገላ. 2፥15፤ ኤፌ. 2፥3፤ ያዕ. 3፥7፤ ይኸው ተመሳሳይ ቃል (φύσις) በአማርኛ ፍጥረት እየተባለ ተተርጕሞአል። ፍጥረት ውስጣዊ ማንነት ነው። ባሕርይን በሚገባ ይገልጠዋል። ደስታ ተክለ ወልድ ባሕርይን ሲተረጕሙ፥ ‘ያልተፈጠረ፥ የማይመረመር፥ የማይታወቅ፥ ኅቡእ፥ ረቂቅ፥ ቅድስት ሥላሴን አንድ የሚያደርግ፥ በሥርው፥ በጕንድ፥ በነቅዕ የተመሰለ፤ የፈጣሪ ባሕርይ፤ አምላክነት’ ይሉታል። ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 162። ከላይ ባየናቸው ጥቅሶች ውስጥ ባሕርይ የሚለው ውስጣዊ ማንነት ወይም ኹነትን ነው።
ቀደም ሲል በነገረ ክርስቶስ እና በነገረ ሰብዕ፥ የባሕርይ ልጅ እና የጸጋ ልጅ የሚለውን ስንመለከት የባሕርይ ልጅ ሲባል ከአድራጊው ጋር አንድ መሆንን አመልካች ነው። ይህ ለኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የምንጠቀምበት የስነ መለኮት ቃል ወይም ሐረግ ነው። ባሕርይ የሚለው ቃል በአንዳንዶቹ φύσις የሚለው ቃል በተተረጎመባቸው ቦታዎች ተፈጥሮ ቢባልም፥ ለመለኮት ተፈጥሮ እንዳንለው ማሰብ አይመችም። ኢየሱስ ፍጡር አይደለምና የተፈጥሮ ልጅ አይባልም። ሥሪት እንዳይባልም እርሱ ሠሪ እንጂ ተሠሪ አይደለምና ይህም አያስኬድም። ኢየሱስ የባሕርይ ልጅ መሰኘቱ ወልድ እና አብ አንድ ባሕርይ ወይም በእንግሊዝኛ essence በግሪክ οὐσία ወይም ούσιος የተባለውን መሆናቸውንና የኒቅያው ጉባኤ አብ እና ወልድ አንድ ባሕርይ ὁμοούσιος ሆሞኡሲዮስ ወይም ὁμοούσιον ሆኖኡሲዮን መሆናቸውን ለመግለጥ እንደተጠቀመበት ተመልክተናል።
ቃሉ አንድ ዓይነትነትን ገላጭ ነው። ὁμός ሆሞ ወይም ሆሞስ አንድ ወይም አንድ ዓይነት ወይም ምንም ልዩነት የሌለው ተመሳሳይ፥ οὐσία ኡሲያ ባሕርይ። ይህንን ὁμοούσιος የሚለውን ሐረግ ወደ እንግሊዝኛ "consubstantial" ብለው ነው የተረጎሙት። ይህ የኒቅያ ጉባኤ አርዮስ የተወገዘበት ጉባኤ ነው። አርዮስ ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ወይም እኩል ያልሆነ ከሰው የሚበልጥ ከአብ ግን ያነሰ ወይም ሙሉ መለኮት ያልሆነ ያደርገዋል። (አርዮሳውያን የሆኑ የዘመናችን የዋችታወር ተከታዮች ወይም የይሆዋ ምስክሮች ነን የሚሉ ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ወይም እኩል ያልሆነ ከሰው የሚበልጥ ከአብ ግን ያነሰ ወይም ሙሉ መለኮት ያልሆነ የተፈጠረ ፈጣሪ ያደርጉታል።) ኋላ በ381ዱ የቁስጥንጥንያ ጉባኤም ይኸው መግለጫ ጸና።
ክፍል አምስትና የመጨረሻው ይቀጥላል።
ዘላለም መንግስቱ
እነሆ ቆሜያለሁ፣ HERE I STAND
ሉተር በዊተንበርግ ዮኒቨርስቲ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ 95 አናቅፅቱን ካስቀመጠ በኋላ የተለያዩ ውግዘቶችና ስደቶች ደርሶበታል። ባነሳቸው የተሐድሶ ሃሳቦች የአደባባይ ሙግት እንዲያደርግ በጳጳሱ ወዳጅ ዶ/ር ጆኸን ኤክ ገፋፊነት በሌፕዢግ ከተማ(1519) ተደርጎ ነበር። ሁለቱም ወገኖች ሙግቱን ባያሸንፉም፣ ዶ/ር ጆኸን ማርቲን ሉተር ቤተክርስቲያኒቱና ጳጳሱ መሳሳታቸውን እንደሚቀበል እንዲናገር አድርጎት ነበር። ይህ ደግሞ ጳጳሱና የቤተክርስቲያን "ካውንስል" የማይሳሳቱ መሆናቸውን መካድ ጭምር ነበር። ቤተክርስቲያን ተሳስታለች ማለት በሞት የሚያስቀጣ ክስ ነው። በተመሳሳይ ውንጀላ ጆን ሁስ ከመቶ አመታት በፊት በእሳት አቃጥለው እንደገደሉት ልብ ይሏል።
ዶ/ር ኤክ ወደ ሮም በመሄድ ሉተርን excommunicate የሚያስደርግ ደብዳቤ እንዳሰበው በፍጥነት ባይሆንም በጳጳሱ ማሕተም የተፃፈ ይዞ መጣ። ደብዳቤው ሲጀምር " Arise, O Lord, and judge thine own cause.... A wild boar invaded thy vinyard." ይል ነበር። ሉተርም ደብዳቤው በደረሰው ስድሳ ቀናት እንዲያስተባብል ጥሪ ቢቀርብለትም ሳይቀበለው ቀረ።
ልዑል ፍሬድሪክ (አስተዋዩ) የሚወደውን መነኩሴና ፕሮፌሰር አሳልፎ ለመስጠት አልወደደም። አብዛኛው የጀርመን ህዝብም ከጳጳሱ ይልቅ ከሉተር ጋር ወገንተኝነታቸውን አሳዮ። በዚህም ምክንያት ሉተር ከሚኖርበት አካባቢ ውጪ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ጳጳሱ የፃፉለትን ደብዳቤና ሌሎች የካቶሊክ ህግጋት(ቀኖና) መጽሐፍትን ህዝብ በተሰበሰበበት በማቃጠልና የሚያምንበትን እምነት አስረጂ ጽሁፎችን መበተን ጀመረ። ምስጋና ለማተሚያ ማሽን ይግባና የምካቴ ጽሁፎቹ በፍጥነት ጀርመናዊያን እጅ ለመግባት በመቻላቸው ማህበረሰቡ እያንዳንዱን ጽሁፎቹን ሸሽጎ ለማኖር አልቸገረውም።
HERE I STAND!
የቤተክርስቲያን ጉዳይ የነበረው ቀስ በቀስ ፖለቲካዊ ይዘት መያዝ ጀመረ፣ ልዑል ፍሬድሪክ የጳጳሱን ቀጥተኛ ትእዛዝ አለመቀበሉን ልብ ይሏል። ጳጳሱ የስፔን ንጉስ የሆነውንና በወቅቱ የጀርመንም ንጉስ የሆነውን ቻርልስ አራተኛን የሆነ እርምጃ እንዲወስድ ግድ አሉት። ንጉሱም ከፈረንሳይ ንጉስ ጋር ላለበት ጦርነት የጳጳሱን ድጋፋ ይሻ ስለነበር ለመስማማት አላንገራገረም። በዚህ ላይ ደግሞ አክራሪ ካቶሊክና የቤተክርስቲያን መተቸት የማያስደስተው ነበር። በተቃራኒው ደግሞ ንጉሰ ነገስት እንዲሆን የመረጡትን የጀርመን ልዑላንን ማስከፋት አልፈለገም። አንዱ ልዑል ደግሞ የሉተር ወዳጅና ጠባቂ ጭምር ነበር።
ንጉስ ቻርልስ አራተኛ ሉተር በዎርምስ በምትገኘው ዲየት (1521) ላይ ለሁሉም ልዑላንና የጀርመን የነፃ ከተሞች መሪዎች ጉባኤ ላይ እንዲገኝና ጉዳዩን እንዲያስረዳ ይጋብዘዋል። ሉተርም ያለመያዝ መብት በማግኘቱ፣ ቢከሰስም እንኳ ወደ ግዛቱ በሰላም እንደሚመለስ ቃል ስለተገባለት ዎርምስ ለመገኘት ሄደ። በወዳጆቹ «ጆን ሁስንም ተመሳሳይ ብለው ነው አቃጥለው የገደሉት» ተብሎ ቢመከርም ዎርምስ ከመገኘት አላገደውም።
በዎርምሱ ጉባዔ ሉተር የጻፋቸውን መጽሐፍት በጠረጴዛ አስቀምጠው አሳይተውት ያለውን ነገር እንዲክድ ጠየቁት። ደግሞስ ከቀደምት ስነመለኮታውያን በላይ አስባለሁ ብለህ የምትለው ማን ስለሆንክ ነው ብለው አበሻቀጡት።
ነገር ግን ማርቲን ሉተር እስከ ዎርምሱ ስብሰባ ቀን ድረስ የተናገረውን አልክድም ለማለት ይህንን ተናገረ፦
"I cannot and will not recant anything, for to act against conscience is neither safe for us, nor open to us. Here I stand, I can do no other. God help me. Amen."
ሲተረጎም፦ «ስቻለሁ የምለው አንዳች ነገር የለኝም፤ ኅሊናዬ ከሚያዘኝ ውጪ መሆን ትክክልም ሆነ አግባብ አይደለም። እነሆ፤ እዚሁ ቆሜያለሁ፤ ከዚህ ውጪ ምንም ላደርግም አይቻለኝም። እግዚአብሔር ሆይ እርዳኝ። አሜን።»
የመዳን መንገድ ክርስቶስ ብቻ፣ እንዲያው በፀጋ ብቻ፣ በእምነት ብቻ የሚገኝ ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የሚሆን፤ የቤተክርስቲያንም ሆነ የቅዱሳን የበላይ ቅዱስ ቃሉ ብቻ የሚለው ሃሳቡን ለማጠፋ/ለመለወጥ ፋቃደኛ ባለመሆኑ ንጉስ ፈረደበት። ንጉሱ ቃል የገባውን በማክበር ወደ ቤቱ በሰላም እንዲመለስ ቢያደርገውም የትኛውም ህግ ለሉተር ከለላ እንደማይሰጠው ወስኖበት ነበር።
መውጫ
ተሐድሶ ብቻ መቆምን ይጠይቃል። ዘመንን መረዳትን፣ መጽሐፍትን መመርመርን፣ ለእግዚአብሔርና ለህሊናችን ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። ተሐድሶ ወደ አባቶችና አያቶች ለመንፀሪያ መመልከትን አንደ ቄንጥ አያይም። የድነትን መኸከለኛ፣ የእምነትን ፈፃሚ፣ የእግዚአብሔርን መገለጥ፣ ትምሕርተ ክርስቶስን አደብዛዥን ሁሉ ለመቃወም ሁለቴ አያስብም። ተሐድሶ ቃለ–እግዚአብሔር ማሕደረ–ክርስቶስ በተባለችው ቤተክርስቲያን ሲደፈጠጥ ጥሪውን በማማ ላይ ያሰማል፤ እነሆኝ ለህሊናዬም ለቃሉም ቆሜያለሁ ይላል። እግዚአብሔር ልጁን በገለጠበት ቃል በኩል ለኅሊናዬ ብቻዬን እንኳን ቢሆን እቆማለሁ የሚል እውነትና ፅናት ያድለን።
ቅዱሳት መጽሐፍት ለሚሉት ብቻ መገዛት ለእግዚአብሔር መገዛት ነው!
#HERE_I_STAND
#እነሆ_ቆሜያለሁ
#ተሐድሶው_ሲታወስ
አማኑኤል አሰግድ
ረድኤታችን የሆንከው ጌታችን ሆይ፣ “ክብርህን ተጠሚዎች፣ ለራሳቸው ፈቃድ የሞቱ ባሪያዎችና ታማኝ የወንጌል ዐደራ ጠባቂዎች አድርገን። በመከራችን ደግሞ ጸጋህን አብዛልን”። አሜን!
* ተስፋፍቶ በድጋሚ የቀረበ *
በ Girma Bekele (ዶ/ር) የተጻፈ።
#ተሐድሶው_ሲታወስ
#ጆን_ካልቪ
በዚህ “ሁሉ” ውስጥ - ግዙፋንና ረቂቃን፣ ያለፈው፣ የአሁኑና የሚመጣው ታሪክ ሁሉ ተካተዋል! በዚህ ምድር ላይ "ጽኑዕነታቸው" እንደ ተራራ የተመሰሉ ኀይላት (ሕዝቦች፣ ፓለቲካም እኮኖሚም) ሲናወጡ፣ ከዐቅማቸው በላይ በሆነ ጉልበት ሲብረከረኩና ሲናዋጡ፣ እግዚአብሔርን መጠጊያ ያደረገ ግን ተስፋው ጽኑ ነው። ምክንያቱም እምነቱ ያረፈው በማይናጠው ልዑል ላይ ነውና! እርሱ “ውሆችን በዕፍኙ የሰፈረ፣ ሰማያትን በስንዝሩ የለካ፣ የምድርን ዐፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣ ተራሮችን በሚዛን፣ ኰረብቶችንም በመድሎት የመዘነ” ነውና (ኢሳ 40:12)። በአጭሩ ዳዊት፣ በሸምበቆ ጥንካሬ አትደገፉ ነው የሚለን!
⏸ ሴላ - Selah (ቆም በሎ ማስብ - pause) - ዳዊት ቆም ብሎ ያስባል። መዝሙሩ በአንድ ትንፋሽ ሳይሆን፣ ሦስት ጊዚ (ቁጥር 3፣ 7፣ 11) ቆም ብሎ በማሰብና በአንሰልስሎት የተዘመረ ነው። ዳዊት በዚህ የሚናወጥ ዓለም የዋስትናውንና የደስታውን ምንጭ ቆም ብሎ ያስባል። በሚናወጠው ዓለም ውስጥ መኖራችን የማይካድ እውነት የሆነውን ያኽል፣ በዚህ ነውጥ ውስጥ የእግዚአብሔር አብሮነት ደግሞ የማይካድ የእውነቶች ሁሉ እውነት ነው። የዚህም እውነት እርግጠኝነት በሰላምና የደስታ ወንዝ ተምሳሌነት ተገልጧል። “የእግዚአብሔርን ከተማ፣ የልዑልን የተቀደሰ ማደሪያ ደስ የሚያሰኝ የወንዝ ፈሳሾች አሉ”። (ቁ. 4)። በሕዝቦች ዐመፅ፣ በመንግሥታት መውደቅና በምድር መቅለጥ በተገለጸው መናወጥ ውስጥ፣ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም በመካከል አለ። "እግዚአብሔር በመካከሏ ነው፤ አትናወጥም፤ አምላክ በማለዳ ይረዳታል" (ቁ.5)
⏸ ሴላ - Selah (ሌላ ቆም በሎ ማስብ) “ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደሆንሁ ዕወቁ” - አሁን ተናጋሪው እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ነው! "ዕረፉ" (ቁ.10) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ራፋኽ ( רפה - râphâh) የሚያሳያን፣ ራስን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ሁሉን ገዢነት አሳልፎ መስጠት፣ በእርሱ ላይ መውደቅ። እርሱ (1) ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል። ማለትም በሁሉ አቅጣጫ የተነሣን ጦርነት ማስወገድ የሚችል እሱ ብቻ ነው። (2) ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል። ይኽም ማለት የጉዳትና የጥፋት መሣሪያዎችን ዐቅም ያመክናል ማለት ነው። (3) ይህ አምላክ - ያህዌ - ጅማሪም ፍጻሜም የሌለው፣ ያለና የነበረ፣ ሁልጊዜም የአሁን አምላክ ነው። ሌሎች አማልክት ምንጫቸው ከሚናወጠው ዓለም ሰለሆነ ከንቱ ናቸው! (4) ይህ አምላክ የሰራዊት አምላክ፤ የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት ሁሉ መገኛና ገዢ፣ የያዕቆብ አምላክ፣ የእኛም አምላክ ነው። “የያዕቆብ አምላክነት"፣ ወሰን የሌለውን የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና የተትረፈረፈ ጸጋ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን “የቅርብ ረዳትነት” ያሳያል። መዝሙሩ በዝምታ በማሰብ ነው። ይህ ፈርጀ ብዙ ነውጥ የበዛበትም ዘመን ለእኛም ሴላ - ቆም የማሰብና የሕይወትን መዝሙር የመቃኘት ወቅት ይሁንልን።
በጽኑ መከራ ውስጥ እያለፋችሁ በታማኝነትና በትጋት ለምታገለግሉ ሁሉ - ሉተር እንደ ዘመረው በርግጥ እግዚአብሔር የማይናወጥ አምባ፣ ዐለትና መጠጊያ ነው! ብድራታችሁ ታላቅ ነውና፣ በርቱ፤ ዘምሩም - አምባችን አምላካችን ነው።
“ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ። ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሁሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ።”
(1 ጴጥሮስ 4:13, 19)
አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)