ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አስተምህሮ፣ ልምምድና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ-ምግባር በተቃረነ መንገድ በመጓዝ የሚታወቀው "ነቢይ" ዑርበርት ኤንጅል፣ ኢትዮጵያ ገብቷል፤ ግለሰቡ ከመሰሎቹ ጋር በመሆን ሕዝቡን ለማጭበርበር የተዘጋጀ በመሆኑ፣ ለቃሉ እውነት የቆመ ወንጌላዊ አማኝ ሁሉ ድርጊቱን በጽኑ ሊቃወም ይገባል።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት።
የታሪክ ባለቤትና ጌታ የሆነው ልዑል እግዚአብሔር፣ ልክ እንደ ተናገረው፣ የ ሰባው ዓመት የግዞት መጠናነቀቂያ ዋዜማ ላይ የፋርስን ንጉሥ ቂሮስን በማስነሣት የባቢሎንን ትዕቢትና ኩራት ሰበረ። ቀደም ሲል ኩራተኛውንና የልዑል አምላክን ክንድ በንቀት የተመለከተውን የአሦር ዓለም ዐቀፋዊ ኀይል በባቢሎንን በማስነሣት እንዳዋረደው ማለት ነው! የኪዳኑን ሕዝብ ብሔራዊ ሉዓላዊነቱን አጥቶ ከወደቀበት መንፈሳዊ ቅውስ ውስጥ አወጣ። ታሪኩ ቀጠለ፤ መሲሑም የመጣው ከዚሁ ተሐድሶ ካገኘ የተበላሸ ታሪክ ውስጥ ነው። እግዚአብሔር ስለ ቂሮስ፦ “ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቻለሁ፤ መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤ ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤ ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣ ነጻ ያወጣል፤” (ኢሳ. 45፥13) ሲል የተናገረውን ፈጸመ።
አቤቱ አምላክችን ሆይ፣ በምሕረትህ ብዛት መልሰህ አብጀን!
~ አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
ከሠላሣ ዓነታት በፊት ኢህአዴግ ለብሔር ብሔረሰቦች “አመጣሁልህ” ካለው ፖለቲካዊ የብሔር ነጻነትና የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን መብት ካለው ጋር “አይጠቅመኝም፥ ከእምነቴ ጋር አብሮ አይሄድም፥ ከአምላኬ ጋር ያጣላኛል” ብሎ ወደጣላቸው ግሳንግሶች አማኙን የሚመልሱ ተግባራት ዘው ብለው ገብተዋል። በኔ በኩል ዘመን አሥሬ ቢለወጥ በየሠፈሩ ቢለወጥ እኔ ምን ቸገረኝ? ለእያንዳንዱ ብሔር እንደ ካድሬዎች ኮብራ ዘመን መለወጫ ቢታደል ምን ይከፋኛል? በዓሎቹ የሚያስከትሉት ዓለማዊ ልምምዶች መኖራቸው ሰይጣናዊ ሥርዓቶችም ተያይዘው መገኘታቸው ግን አስጸያፊ ነገር መሆኑ ለዚህ ጽሁፍ ቀስቅሶኛል። ማኅብረሰቡ ፋብሪካ ሲል፣ የኢንዱስትሪ ዞን ሲል፥ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ሲል፥ ሊስትሮና ሎተሪ ይዘው በየከተሞች ለሚንከራተቱት ሕጻናት የትምህርት ዕድል ሲል፥ ለልመና መንገድ ዳር ለሚጓተቱ አሮጊቶችና አዛውንቶች መጠለያ ሲል፥ ከጦር ሜዳ አካላቸውን አጥተው ለተመለሱት ወታደሮች ጡረታ ሲል፥ በየሆቴሉ ራሳቸውን ሽጠው ለሚኖሩ ለበሽታና ለሞት ለሚጋለጡ ሴቶች ሌላ የሥራ መስኮት ወዘተ … ሲል ለ አካባቢው ማኅበረሰብ ወፍ የለም። የዘመን መለወጫ ግን በየመንደሩ ታድሎአል። እየወጣህ ጨፍር ተብሏል።
ማደንዘዣ ነው። ከቅዱስ ቃሉ ትምህርት ይለይሃል።
ማርከሻ ነው። አትምሰል ከተባልኼው ጋር ያመሳስልሃል።
የእምነት እሴቶችህን ያፈርስብሃል። ሰይጣናዊ ነው።
ጨረስኩ።
ወርቅነህ ኮየራ
የመከራ ስነ መለኮት፤ ክፍል ሦስት፤
መከራ እንዴትና ለምን ሊኖር በቃ?
ይህ ክፍል ወደ ውድቀት ጠንቅ ይመራናል። ውድቀት ማለት አዳም የወደቀበት የመጀመሪያው ኃጢአት ነው። መከራ የኖረው ከውድቀት የተነሣ ነው። ውድቀት የኖረው ደግሞ ከነፃ ፈቃድ የተነሣ ነው። ነፃ ፈቃድ ሳይኖር ውድቀት ቢኖር ኖሮ፥ ነፃ ፈቃድ የሌለው ሰው ኃጢአት ስለሠራ፥ ተጠያቂው እግዚአብሔር ይሆናል።
‘ሰው እንደሚወድቅ የሚያውቅ አምላክ የሚወድቅ ሰውን መፍጠሩ ሲጀመርስ ጥበብ ነውን?’ ብለው የሚጠይቁ አሉ። ጥሩ ጥያቄ ነው። የሚወድቅ ፍጡርን መፍጠሩ ጥበብ ካልሆነ ሌላው አማራጭ ምን ሊሆን ነው? ሌላው አማራጭ፥ ወይ መምረጥ የማይችል ፍጡርን መፍጠር፥ ወይም ጭራሹኑ አለመፍጠር ነው።
ነፃ ፈቃድ የሌለው ሰው ደግሞ እንደ አሻንጉሊት ወይም ሮቦት የተገጠመለትንና እንዲያደርግ የተሠራለትን ሥራ ብቻ ያደርጋል እንጂ መምረጥ አይችልም። እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ደግሞ ለሰው ለራሱ ጥቅም ከፈጣሪው ጋር ኅብረትን በማድረግ ይደሰት ዘንድ ነውና፥ ከፈጠረ ነፃ ፈቃድ ያለውን ሰው መፍጠሩ ሞራላዊ ግዴታ ነው። የመጀመሪያው ሰው ይህንን ነፃነቱን ሲተገብር እግዚአብሔርን መታዘዝን ትቶ የተከለከለውን በማድረግ እግዚአብሔርንና ቃሉን ናቀ፤ ተላለፈም። ታሪኩ በዘፍ. 3 ይገኛል። እግዚአብሔር ፍጹም ቅድስናን የተላበሰ ቅዱስ ነውና ቅንጣትም ኃጢአት ባለበት ኅብረት ሊኖር አይችልምና ሰውና እግዚአብሔር ተለያዩ።
የሰውን ውድቀት ተከትሎ የኃጢአት መዘዝ የሆነው የተፈጥሮ መዛባት፥ የሰው ጭንቅና ስቃይ፥ በሌላው ላይ መክፋት ተከተለ። መከራና ሞት የውድቀት መዘዞች ናቸው እንጂ ሰማይና ምድር፥ ፍጥረታትና ሰው ሲፈጠሩ አብረው የተፈጠሩ ነገሮች አይደሉም። ሰው ከዔድን ገነት ከመውጣቱ በፊት ፍርድ ተበየነ፤ ቅጣት ተፈጸመ፤ ከወጣ በኋላም ብልሽቱ ቀጠለ። የኃጢአት እና የመዘዞቹ መኖር እግዚአብሔርን ተጠያቂ አያደርገውም። አንድ ነገር እንዳይሆን አላደረገም ወይም አልከለከለም ማለት እግዚአብሔር በዚያ ነገር መሆን ወይም መፈጸም ተስማምቷል ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ሉዓላዊ አምላክ ቢሆንም በሰዎች ፈቃድ ላይ ግዴታን አይጭንም።
እግዚአብሔር አንድ ነገር እንዳይሆን አላደረገም ማለት በዚያ ነገር ተስማምቷል ወይም ፈቅዷል ማለት አይደለም። በአንጻሩ ደግሞ፥ ወደ ቅዱሳኑ የሚመጣ ማናቸውም ነገር ያለ እርሱ ፈቃድና እርሱ ሳያውቅ ይመጣል ማለትም አይደለም። አንዳንድ መከራዎችና ፈተናዎች በራሱ በእግዚአብሔር ፈቃድ እና በራሱ በእግዚአብሔርም ወደ ቅዱሳን ይመጣሉ። እንዲህ ከሆነ እነዚህ ፈተናዎችና መከራዎች ሥራና ግብ አላቸው ማለት ነው። ይህ እውነት ቅዱሳንን ግር ሊያሰኝ ይቻል እንጂ ግን እውነት ነው።
ሁላችንም ከልባችን ስር የምናውቀው እውነትና የማንክደው ሐቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ግንኙነት የሚልቀውና የሚጠነክረው በድሎትና በቅንጦት ስንሆን ሳይሆን በፈተናና በመከራ ውስጥ ስናልፍ ነው። ያ ጊዜ የምንጾምበትና የምንጸልይበት፥ እርሱን ለመምሰል የምንጥርበትና በተወልን ምሳሌነት የምንሄድበት ጊዜ ነው። መንፈሳዊ ማንነታችን ተፈልቅቆ ይወጣል። ምንም ይሁን፥ ምንም ይምጣ፥ ከፊቱ ላንጠፋ፥ ከቤቱ ላንወጣ የምንምልበት ጊዜ ነው።
ኢዮብ ቀድሞም መንፈሳዊ ሰው ነው። የደረሰበት ለምን እንደሆነ ሳይገባውም፥ ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥ ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ። እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ። አለ፤ ኢዮ 13፥14-15። ይህ ሰው ሲጨልምበት እየደመቀ መጣ። እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ ያለው ሰው፥ የትዕግሥት ምሳሌም ሆነ፤ ያዕ. 5፥11። በምንም የሰው መለኪያ ብንሰፍረው እኮ ኢዮብ የሆነበት ሁሉ ሊሆንበት የተገባው ሰው አይደለም። ደግነቱ መለኪያችን የሰው መለኪያ ብቻ ነው፤ የወደቀ ሰው መለኪያ።
በዮሐ. 15፥2 እንደተጻፈው፥ ሲያጠራን ብዙ ፍሬ እንድናፈራ ነው። ማጥራት መግረዝ ነው። ፈተና መከራና ስቃይ በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ያሉ መቅረጫ መሳሪያዎች ናቸው። ልጁን እንድንመስል፥ ፍለጋውን እንድንከተል የሚያደርጉን መሳሪያዎች ናቸው። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። 1ጴጥ. 2፥21። ምሳሌ ትቶልን ስለ እኛ መከራ የተቀበለው፥ እኛ ስለ ሌሎች መከራ ባንቀበልም፥ ለሌሎች አርዓያ ልንሆን፥ ምሳሌውን እንድንከተል ነው።
ይቀጥላል።
ዘ. መ.
የመከራ ስነ መለኮት፤ ክፍል ሁለት፤
እግዚአብሔር አለ? ከኖረስ፥ መልካምና ሁሉን ቻይ ነው?
በክፍል አንድ ቅምጥልነት በሚሰበክበት ቄንጠኛ ዘመን መከራን መስበክ ኋላ ቀርነት ሊመስል እንደሚችል ብያለሁ። ከእውነት መሸሽ እንችል ይሆናል እንጂ ማምለጥ አንችልም። ‘እህ! እርሱ ቆስሎልኝ እኔ ለምን እታመማለሁ?’ ያለ ደፋር በቅርብ አሜሪካ መጥቶ ሲታከም ብትሰሙ መሳቀቅ የለባችሁም! ከእውነትና ከእውነታ ሲሸሹ ቆይተው U-Turn ሠርተው የተመለሱ ጥቂት አይደሉም። የጎዷቸው ግን ብዙዎች ናቸው።
የመከራና ጭንቅ፥ የስቃይና ጉስቍልና፥ የስደትና ፈተና በዚህች ምድር እና በዚህ ሕይወት መኖር እና የእግዚአብሔር መልካምነትና ሁሉን ቻይነት አብረው ይሄዳሉ? ይህ የኖረ፥ ያረጀ ጥያቄ ነው። ከሐዲዎች አለመኖሩን ለማሳየት ዘብተው በስላቅ ጠይቀውታል፤ ፈላስፎችም፥ ሊቃውንትም፥ ተርታ ሰዎችም ጠይቀውታል፤ ሃይማኖታውያንና ሃይማኖተኞችም ጠይቀውታል፤ ስነ መለኮታዊ ጉዳይም ነውና ክርስቲያኖችም በትሕትና ጠይቀውታል። መልካም ከሆነ ለምን ስቃይ ኖረ? ሁሉን ቻይ ከሆነ ለምን አላስወገደውም? ጠያቂዎቹን እሦስት እንክፈላቸው።
1. እግዚአብሔር የለም የሚሉ ከሐድያንና ዓለምተኛ ፍልስፍናዎች፥ ‘እንደምትሉት ዓይነት መልካምና ሁሉን ቻይ አምላክ ቢኖር ኖሮ ይህ ሁሉ ሰቆቃና ስቃይ ለምን ኖረ? እርሱ ቢኖር ኖሮ ይህ ሲሆን ዝም አይልም፤ ወይም ማለት አልነበረበትም፤ ስለዚህ የለም።’ ይላሉ። ‘ታድያ ለምን ኖረ? እንዴት ኖረ?’ ተብለው ሲጠየቁ፥ ‘ትልቁ ትንሹን ማጥቃቱ፥ መዋጡ የተፈጥሮ ሕግ ነው፤ የተሻለው ዝርያ ሊኖርና ሊቀጥል መንገዱ survival of the fittest ነው ይላሉ፤ ዳርዊን ምስጋና ይግባውና። ስለ ሌላው ሲል ጥቃትን፥ ስቃይን በፈቃዱ ስለሚቀበለው ሰው ሲጠየቁ ላብ ያሰምጣቸዋል፤ በእነርሱ ሃይማኖት (ሃይማኖት መሆኑን ባይቀበሉትም) የተፈጥሮ ሕግ አይደለማ!
2. ሃይማኖታውያኑ ደግሞ፥ ‘እግዚአብሔር አለ፤ ግን . . .’ ይሉና፥ አንዳንዶቹ እንደ deistቶች ያሉት፥ ‘እርሱ አለ እንጂ ለፍጥረቱ ደንታ የለውም፤ ፈጥሯቸው እንደ ፍጥርጥራቸው ይሁኑ ብሎ ትቷቸዋል፤ ክፋትም ደግነትም የሰው ሥራዎች ብቻ ናቸው።’ ይላሉ። ሌሎቹ፥ ‘እግዚአብሔር አለ፤ አቅምም አለው፤ ግን መልካም አይደለም፤ ጨካኝ ነው።’ ሲሉ የነዚህ አጸፈኞች ደግሞ፥ ‘እግዚአብሔር ጨካኝ አይደለም፤ መልካም ነው፤ ግን ሁሉን ቻይ አይደለም።’ ይላሉ። ክፉም ደግም አያደርግም የሚሉም አሉ፤ በልባቸውም፦ እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፥ ክፉም አያደርግም የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ። ሶፎ. 1፥12።
3. ሦስተኞቹ እኛ ነን፤ መጽሐፍ ቅዱሳውያን ክርስቲያኖች። እግዚአብሔር መልካም መሆኑን፥ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ከልባችን እስከ እንጥፍጣፊው ድረስ እናምናለን። በምድር የክፋትን መኖር እናምናለን፤ እንቀበላለን። ይህ በየቀኑ የምናየውና የምንሰማው ጉዳይ ነውና አለመቀበል አይታሰብም። ቃሉም ክፋት በምድር መኖሩን ይመሰክራል። ቅዱሳን ስሞታ አቅርበውበታል፤ ዳዊት፥ ኤርምያስ፥ ዕንባቆም፥ ጳውሎስ፥ ወዘተ፥ ጥቂቶቹ ናቸው።
እርግጥ ምድራችን አሁን ባለችበት መልኳና ሁኔታዋ ተፈጥራ ቢሆን ኖሮ፥ ‘እግዚአብሔር መልካም አይደለም’ ማለት ይቻል ይሆናል። ‘ይቻል ይሆናል’ ስል አሁን ባለችበት የተበላሸ መልኳም እንኳ ክፋት ብቻ ሳይሆን መልካምም ስለሚገኝ፥ ስለ መልካሙ ብቻ እንኳ፥ ‘እግዚአብሔር መልካም ነው።’ መባል ስለሚቻልና ስላለበት ነው።
አሁን ያለውን የምድራችንን ሁኔታ አይቶ፥ ‘እነሆ ሁሉ እጅግ መልካም’ ማለት አይቻልም፤ ወይም ከባድ ነው፤ ወይም ቀላል አይደለም። ምድራችን በውስጧ ካሉት ጋር ብዙ ትራፊ ውበት ቢኖርባትም ሰንበሯና ጠባሳዋ የሚያሳብቀው ብዙ ሰብቅ አለ። የተፈጥሮ መከራዎች፥ የወንዝ ሙላት፥ ጎርፍ፥ ሱናሚ፥ የመሬት መንሸራተት፥ መደርመስ፥ መንቀጥቀጥ፥ እሳተ ገሞራ፥ ድርቅ፥ የአራዊት አስፈሪነት፥ ወዘተ፥ እንዲሁም ሰውም ብዙ መልካምነት ቢኖረውም፥ ሰው ሠራሽ ሰቆቃዎች፥ ክፋት፥ ጭካኔ፥ ግፍ፥ ጭቆና፥ የፍርድ ጥመት፥ ጦርነት፥ የነፍስ ግድያ፥ ዝርፊያ፥ ብዝበዛ፥ ተላላፊ በሽታዎች፥ ወረርሽኞች፥ ወዘተ፥ በዚህ ሁሉ መልኳ ስትታይ ዓለማችንን በዚህ ዓይነት መልክና ሁኔታ የፈጠራት ፈጣሪ መልካም አይደለም መባል ይቻል ይሆናል።
ግን፥ ዓለም/ምድር ስትፈጠር እንዲህ ነበር ወይ? #አይደለም። ‘አይደለም’ የሚለው ቃል ደምቆ ይሰመርበት። የአሁን የምድራችን መልክና ሁኔታ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን፥ ግዑዛንና ሕያዋን ፍጥረታትን ፈጥሮአቸው በነበረበት መልክ አይደለም። ሁሉን ከፈጠረ በኋላ በስድስተኛው ቀን፥ ሁሉንም አይቶ፥ እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። አለ፤ ዘፍ. 1፥31። ታድያ፥ መከራና የመከራ ስነ መለኮት እንዴት ተፈጠረ?
ይቀጥላል።
ዘ. መ.
2️⃣ በእውነተኛና በፍሬ በሚገለጥ ንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስ። ይህም ማለት የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው “የውደቀታችን ጥልቀት መረዳት፣ መመለስና ወደ ቀናው መንገድ መመለስ” ማለት ነው። “እንግዲህ ከየት እንደ ወደቅህ ዐስብ፤ ንስሓ ገብተህ ቀድሞ ታደርገው የነበረውን ነገር አድርግ” (ራእይ 2፥5) የእግዚአብሔር የምሕረት ደጆች አልተዘጉም። ፈሪሓ እግዚአብሔርን ከረገጥን፣ ምን ተስፋ አለን? ስለዚህ በግልና በጋራ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንድናገኝ በእውነተኛ ንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ።
3️⃣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሸንን ሥራ መደገፍ። የተረዳሁትን ያህል ይህ ኮሚሽን “የልብን ጕዳይ” ለመድረስ ጥረት እያደረገ ነው። ፈርጀ ብዙ የመስተጋብር ፈውስ ያስፈልገናል - ከእግዚአብሔርም፤ ከእርስ በእርስም። የታሪክ አረዳድ፣ የአገረ መንገሥት አወቃቀር፣ ሕገ-መንግሥት መሻሻል፣ በፌዴራሊዝምና በክልላዊነት መካከል ሊኖረው ስለሚገባው ሚዛናዊ፣ ጤናማና ተዓማኒነት ያለው ግንኙነት፣ የወሰን ጕድይ፣ ቅቡልነት ያለው የድምፅ ውክልናና ተመሳሳይ ጥያቄች አገራዊ መግባባት ይሻሉ። በፍትሕ፣ በሰላም፣ በይቅር ባይነት፣ በዕርቅና በፈውስ ላይ ወደ ተመሠረተ አገራዊ መግባባት መሄድ ይገባናል። ለሁሉም ቅን ምክክር ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ በዋነኛነት የልብ ፈውስን ይጠይቃል። ብዙ ነውጥ ባለባት አገር ኮሚሽኑ ሥራውን የሚያስተጓጉሉ ብዙ ችግሮች ሊኖር እንደሚችሉ እገምታለሁ። ቅዱስ ቃሉ፣“የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” (ምሳሌ 13፥12) እንደሚል፣ የሕዝብ ልብ እንዳይዘል ሥራውን በፍጥነት መጀመሩና ከመንግሥት፣ ተቃዋሚዎች፣ ከቤተ እምነቶችና ከአገር ሽማግሌዎችና ምሑራ ማኅበረ ሰብ በሙሉ ያልተቆጠበ ትብብር ማግኘቱ እጅግ አስፈላጊ ነው።
4️⃣ ፓለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን ከዘረኝነት ሊፋቱ ይገባል። “ብሔርተኝነት” የራስን ማንነት ማግዘፍ፣ ሌላውን ማኮሰስ ብቻ ሳይሆን፣ የሰውን አምሳለ አምላክ ተሸካሚነት መግፈፍ ነው። ሰው ክቡር ነው። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነውና! ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ የትኛውም ግዛት ያለስጋት እንዲኖርና የምድሪቱም በረከት እኩል ተካፋይ እንዲሆን የሚያስችል የእውነተኛ የሰብዓዊነት ተሓድሶ ያስፈልገናል። “እኔነትን” መካከለኛ ያደረጉ የጥላቻ፣ የፍርሃት ያለመተማመንና የአግላይነት ግድግዳዎችን ማፍረስ። የኢትዮጵያዊነት ፋይዳ ልክ ከኅብረ ቀለም እንደ ተሠራ ጥልፍ፣ ከልዩ ልዩ ብሔረሰባዊ መለያዎቻ (ባሕልና ቋንቋ) የተበጀ ጌጥ ነው። በጥምረት ያስተሳሰሩን ትውልድ ተሻጋሪ ፋይዳዎቻችን፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶቻችንን አልፈው መታየት ይኖርባቸዋል።
5️⃣ በአሁኑ ወቅት በግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ፣ መንግሥትን ጨምሮ ሰይፋቸውን ወደ ሰገባው መልሰው ወደ ውይይት መመለስ። የዐመፅ ዑድት የመስበሪያው መንገድ ይኸው ብቻ ነው። የእስከአሁኑ አካሄዳችን አድካሚ፣ አክሳሪና መከራ ያጨድንበት ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚል፣ “መንግሥት “ለመልካም ነገር የሕዝብ አገልጋይ” ነው (ሮሜ. 13፥4)። የመንግሥት አወቃቀር፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደር መርሕ፣ ፍትሐዊነትና ተኣማኒነት የሚገለካወ በዚሁ እውነት ነው። ቅቡልነቱ ሲጐዳና የሕዝብ ልብ ሲሸሸው ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። ጦርነትና በማቆም፣ ለምክክር፣ ዕርቅና ሰላም ጥሪ ማድርገ ይገባዋል። የሰው አምሳል መለኮት ተሸካሚነትና ክቡርነት እንዲሁ ሰላም የቤተ እምነቶች ሁሉ የጋራ ዕሴቶች ናቸው። የሃይማኖት መሪዎች፣ ከጭፍን ውገናና ጥላቻ መሣሪያ ከመሆን፣ ለላቀው አምላካዊ ዐደራ በመኖር የዕርቅና የሰላም መንበር ለመኖር ከምንጊዜውም በላይ ወቅቱ አሁን ነው።
እንደ ወንጌላዊ አማኝ የሚከተለውን በመጨመር ዐሳቤን ልደምድም። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ እንደራሴ ናት። የመንግሥትም ኾነ የተቃዋሚ ፓርቲ አይደለችም። እንደ አማራጭ የክርስቶስ ማኅበረሰብ፣ አማኞች በሙሉ የተሻለውን መንገድ የመኖርና የማሳየት ትልቅ ዐደራ አለብን። የክርስቶስን ሥር-ነቀል የጽድቅ መንገድ በመከተል፣ ጨውና ብርሃን ልንሆን ተጠርተናልና። የወንጌል ዐዋጃችን እውነተኛነት፣ ተዓማኒነትና ቅቡልነት የሚለካው ከክርስቶስ ጋር የሚገጥም ሕይወት በኖርንበት መጠን ነው። ክርስቶስ፣ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ፣ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ. 5፥16) እንዳለ፣ በመስቀል የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ሰዎች በእኛ ውስጥ ማየት መቻል አለባቸው። ሕይወት የጐደለው ምስክርነት ዐቅም የሌለው ከንቱ ልፍለፋ ነው። “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷል” ስንል፣ ይህን “ዘርና ማኅበራዊ ድንበር የማያውቅ ንጹሕ መውደድ” ሕዝባችን በእኛ ውስጥ ማግኘት መቻሉ ነው።
እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ፣ አገራችንን በሰላምና በዕርቅ መንገድ ይምራ፤ ከዐመፅ ዑደት ይታደጋት፤ በሰላሙም ይጠብቃት። አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
ሐሰተኛ ነቢያት ስለምን በመካከለኛው ደቡብ በዙ? ክፍል ሦስት (የመጨረሻው)
በክፍል አንድ እና ሁለት በመካከለኛው ደቡብ ሐሰተኞች ነቢያትና ሐዋርያት ለምን በዙ ለሚለው ጥያቄ ሁለት ምክንያቶችን አይተን ነበር። 1ኛው የደቀ መዝሙርነት መጥፋት ነው። የእውነተኛ ክርስትና፥ ራስን መካድ፥ ጌታን መውደድ፥ መስቀል ተሸክሞ ዕለት ዕለት የመከተል ሕይወት መጥፋት ነው። ቤተ ክርስቲያን አሁንም ነቅታ በዚህ ጉዳይ ካልሠራች ይህ ችግር እየባሰ ይሄዳል። 2ኛው ምክንያት ደግሞ ሐዋርያት እና ነቢያት ነን የሚሉት ሐሰተኞች አጭበርባሪና አታላይ ተፈጥሯቸው አሳቾች እንዲሆኑ ማድረጉ ነው። ይህ በመካከለኛው ደቡብ ብቻ ሳይሆን የትም ቢሆኑ አሳቾች አሳቾች ናቸውና ባሕርያቸውን የተመለከተ ነው።
በዚህኛው በሦስተኛውና በመጨረሻው ክፍል ከሁለቱ (ከቤተ ክርስቲያንም፥ ከሐሰተኞቹም) ውጪ ባሉት ለሐሰተኞች መፈልፈል አመቺ ሁኔታ የፈጠሩ ነጥቦችን በመጠነኛ ዝርዝር ብቻ አመለክታለሁ። የሐሰተኞች እሳተ ገሞራ በተሰኘው መጽሐፌ ከገጽ 107-174 ባሉት ገጾች ለሐሰተኛ ነቢያትና ሐዋርያት ፍንዳታ ምክንያቶች ናቸው የምላቸውን 21 ነጥቦች በዝርዝር አቅርቤአለሁ። እዚህ ከዚያ ውስጥ ጥቂት በመውሰድ ሌሎችንም እጨምራለሁ።
1. ይህኛውን የመጀመሪያው ነጥብ ላድርገው። ዘመናችን የመጨረሻው ዘመን። ጌታ ከዳግመኛ መምጣቱ በፊት ስለሚሆኑት ነገሮች በግልጽ አስተምሮአል። ጳውሎስ በ2ጢሞ. 3፥1-9 ስለ መጨረሻው ዘመን መልክ በግልጽና ስዕላዊ በሆነ ቋንቋ ጽፎአል። እነዚህ ሰዎች ሊመጡ ግድ ነው።
2. የሕዝቡ ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ መልክ። ይህ አካባቢ ወንጌል በብዛት የተሰራጨበትና በጠቅላላው የሕዝቡ አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አተያይ ተቃኝቷል። ቢሆንም አሁን ሁለተኛና ሦስተኛ ትውልድ ሆኖ ሃይማኖቱ ልማዳዊ እየሆነ መጥቷል። የሃይማኖት መልክ ኖሮት ኃይሉ የተካደበት ሁኔታ ይታያል። ለአያሌ ዓመታት ኦርቶዶክስ ነን እያልን ስለ ክርስቶስ አዳኝነት ሳይነገረን ያልዳንን ሆነን እንደኖርነው እዚህም እንደዚያ እየሆነ ነው። ልዩነቱ እነዚህ እንደ ክትባት የመሰለ ነገር ተወግተዋል፤ የመጽሐፍ ቅዱስን ቋንቋም መናገር ይችላሉ። በሌሎች የአገራችን ክፍሎች ቢሆኑ ኖሮ መታገሥ የማይቻሉት እነዚህ ሰዎች ይህ አካባቢ አቀፋቸውና አፋፋቸው። ሐሰተኞቹን በተመለከተ ቃሉን ያልተማሩ መሆናቸውን በክፍል ሁለት ጠቅሻለሁ። ሕዝቡ ደግሞ ያልተማሩ አስተማሪዎችን ሳይጠይቅ የሚሰማ፥ ልጋልብህ ሲሉት ጀርባውን ከእግራቸው በታች የሚያነጥፍ ሆነ።
3. የእምነት ቅይጥነት። ሕዝቡ ሃይማኖታዊ ብቻ አይደለም፤ ቅይጥም ነው። ቃልቻም፥ ቆሌም፥ አድባርም፥ ጥንቆላም፥ ውቃቢም፥ ዓይነቱና ብዛቱ መጨረሻ ያለው አይመስልም። ያ ሳይራገፍለት፥ ይህኛው ተጨምሮለት፥ ሕዝቡ ሁለቱንም አዝሎ እየሄደ ይገኛል። ሐሰተኞቹ የሚያደርጓቸው ነገሮች ክርስቲያናዊ ቅርጽና ቋንቋ ቢኖራቸውም ጥንቆላዊ ይዘትም ስላለባቸው ተከታዮቻቸው ከሁለቱም ጎራ ናቸው፤ ለሁለቱም አዲስ አይደለም። አንድ ምሳሌ ላሳይ፤ አንድ ወዳጄ ከ5 ወራት በፊት የጻፈልኝ ነው፤
“አርብ እለት ከሲዳማ በንሳ አካባቢ ከሚመጡ ደንበኞቻችን አንዱ ከ15 ቀን በፊት ከጎረቤቴ እቃ ሲገዛ 6500 ብር ተጭበርብሬአለሁ ይላል አገሩ ላይ የቤተክርስቲያን ሺማጊሌ ነው ከጎረቤቴ ጋር በፍጹም ሊግባቡ አልቻሉም እናም ሽምግልና ተቀመጥን በፍጹም መተማመን ባለመቻላቸው ከሲዳማ የመጣው የቤተክርስቲያን ሽማጊሌ መዛት ጀመረ በሚያሳዝን ሁኔታ ገንዘቤን ካልመለስክልኝ አገሬ ሄጄ አሳቅልብሀለሁ በሞባይሌ ያነሳሁህን ፎቶ አገሬ ላለ ለታወቀ ቃልቻ በማሳየት አንድ ወይፈን ሰጥቼው እንዲያሳብድህ ነው የማደርገው በማለት ተናገረ በጣም ደነገጥን አንተ ክርስቲያን አይደለህም እንዴ አልኩት ለዛው ጽድት ያልኩ ጴንጤ ነኝ አለኝ አብረውት የነበሩ ከሱ አገር የሚመጡ ጓደኞቹ ክርስቲያኖች ናቸው ከነቤተሰቦቻቸው ከቸርች የማይጨፉ በሚያሳዝን ሁኔታ የሰውየው ተባባሪዎች ናቸው ነገሩ ስለከነከነኝ ስለሁኔታው ለማወቅ ብዙ ጥያቄ አነሳሁላቸው ገበያ ሲጠፋ ምርት ሲበላሽ ሰው ሲታመም ሌባ ሲያስቸግራቸው መፍትሄ ወደሚሰጥ የታወቀ ቃልቻ እንደሚሄዱ አጫወቱኝ ጌታስ ክርስትናስ አልኳቸው ለቃልቻው ጥበብ የሰጠው እኮ ጌታ ነው አሉኝ በጣም ነው የደነገጥኩት።
ይህን የምነግርህ ህዝባችን ከእውነት ቃል ከመራቁ የተነሳ ቃልቻ ቤት የሚደረገው ነገር ከጌታ በተሰጠ ጥበብ እንደሆነ እስኪያስቡ ድረስ ተላልፈው ተሰተዋል ። ጋሽ ዘሌ ይህን ሁኔታ ከእኔ ጋር የነበሩ ክርስቲያን ወንድሞች በደንብ ሰምተዋል በጣም የሚያስደነግጥ ነገር ነው የሀሰተኛ ነብያቱ ሲገርመን ገና ያልተገለጡ ጉዶች አሉን ሰዎቻችን ቃልቻ ቤትም ቸርችም ይሄዳሉ።”
እንግዲህ ይህ የሚያሳየው ቅይጣዊነት ሕዝቡን እየወረሰ ያለ መሆኑን ነው። በክፍል ሁለት በለጠፍኩት ላይ ተስፋየሱስ ደግፌ አስተያየት ሲሰጥ፥ ‘የአሁኑ ትውልድ በከፊል በሚባል ደረጃ ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር ወደ ተፋለሰው ባህላዊና መናፍስታዊ መሰል የትንቢት ተግባር ናፋቂ ሆኗል፣ . . .’ ብሏል። ከፖለቲካዊው አንጻር ባህላዊ ሃይማኖት ዘመናዊ ሃይማኖት እየሆነ መምጣቱ ለጥቂቶች የወንበር መጠበቂያ ሲሆን ሕዝቡ ሃይማኖቱም ሲቀየጥ ታጋሽ መሆኑ እየጨመረ መጣ።
4. ጴንጤ ቆስጣዊነት፥ ልምምዳዊነትና ምልክታምነት። ይህ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለማችንም የብዙ ሐሰተኛ ትምህርቶችና ልምምዶች መፈልፈያ መሆኑ የታወቀ ነው። በኢትዮጵያ ጴንጤቆስጣዊ ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚወሱት የመጀመሪያዎቹ ኮንፈረንሶች ይደረጉባቸው የነበሩት ሾኔ እና አዋሳ በዚህ በመካከለኛው ደቡብ የሚገኙ ከተሞች ናቸው። ጴንጤቆስጣዊ ልምምዶች ለአካባቢው እንግዳ አይደሉም። በአካባቢው በስፋት ናኝተው የነበሩትን የቃለ ሕይወት አብያተ ክርስቲያናት የጎደላቸው ልምምድ እንዳለ በማስተማር አጥቢያዎች እየተገለበጡ በጅምላ የተወሰዱባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ከ15 ዓመታት በፊት በወላይታ አንዲት ጴንጤቆስጣዊት ቤተ ክርስቲያን አንድ 'የተሳካ' ዘመቻ ጀምራ ነበር። የቃለ ሕይወት አጥቢያዎች ባሉባቸው ቦታዎች አጠገብ ሄደው አጥቢያ ይከፍታሉ። ከጥቂት ወራት በኋላ ውኃ ከወንዝ በቦይ እንደሚጠለፈው እየጠለፉ መውሰድ ጀመሩ። በሁለት ዓመት ጊዜ ከ40 በላይ አጥቢያዎችን ወደ ራሳቸው አዞሩ። ልምምዳዊነት ችግሩ በቀላሉ የሚኮረጅና የማይፈተሽነቱ ነው። ስለዚህ ውሸታም ፈውሶች፥ ውሸታም ተአምራት፥ ልብ ወለድ ምስክርነቶች፥ የውሸት ተስፋዎችና ትንቢቶች በገፍና በጅምላ ይቀርባሉ። መኮረጅ የሚፈቀደውን ያህል መፈተሽ ይኮነናል፤ ስለዚህ ለመፈተሽና ለመጠየቅ የሚደፍር የለም። ከዚህ ጋር የምልክት ራብተኝነትና ናፋቂነት ሕዝቡን ገዛው። በዚህ ላይ የቃል እምነት ኑፋቄ ተደረበ። እነዚህን በአንድ ከረጢት አደረግኋቸው እንጂ ለየብቻ ሊታዩ የሚችሉ ናቸው።
5. ለመሪ ያለ አክብሮት። በብዙ የአገራችን አካባቢዎች እንደሚደረገው ሁሉ መሪዎች ይከበራሉ። በተለይም መንፈሳዊ መሪዎች እንደ መንፈሳዊ አባት ይቆጠራሉ። በመካከለኛው ደቡብም መሪዎች ይከበራሉ። ቃልቻዎችንና ጠንቋዮችንም ጨምሮ የሃይማኖትና የልማዳዊና ባህላዊ እምነት መሪዎችም ይከበራሉ። ሐሰተኛ ነቢያትም ሐሰተኛነታቸውን ሸፍነው ነቢይ እና ሐዋርያ ተብለው ሲከሰቱ አክብሮትና አድናቆት ይሠዋላቸዋል። ብዙዎቹ ሐሳውያን ከዚህ አድናቆት በመንደርደር ነው ከመካከለኛው ደቡብ ወደ አገሪቱ ዋና ከተማ የተወነጨፉት።
ሐሰተኛ ነቢያት ስለምን በመካከለኛው ደቡብ በዙ? ክፍል አንድ
ሐሰተኛ ነቢያት ከየትም ይመነጫሉ። ሰይጣን የተለየ የችግኝ መደብ የለውም። አንዳንድ ጊዜዎችና ቦታዎች ግን ምቹ መደቦች ይሆኑለታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደተፈለፈሉት ያሉ ሐሳውያን ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ስላልወጡ ያ የአገራችን ክፍል የተባረከና ወንጌል የሮጠበትና የሚሮጥበት ነው ማለት አይደለም። ወይም ምንጫቸው ከዚያ የሆኑ ሐሰተኛ ነቢያት የሉም ማለት አይደለም። ወንጌል በሰሜኑ አገራችን እየተቀበለ ያለው ተግዳሮት የወንጌል ጠላቶች በሆኑ አገሮች ከሚቀበለው ጋር የሚነጻጸር ነው። ጨለማ የወረሳቸው የአገራችን ኪሶችም አእላፋት ናቸው። ሐሰተኞች ሁሉ ደግሞ ከዚያ አንድ አካባቢ ብቻ የፈለቁ አይደሉም። ሐሰተኞች ከመልክዓ ምድራዊ መገኛ አይመነጩም። ከአይሁድ እውነተኛ ነቢያት እንደነበሩ ሐሰተኞችም ነበሩ። ከአሕዛብ ድንቅ አገልጋዮች እንደነበሩ እኵያንም ነበሩ። ነገር ግን ከአንድ አካባቢ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ እንደ አሸን ሲፈሉ ጥያቄ መጠየቅ የግድ ይሆናል። መመርመርና መፈተሽ ተገቢ ይሆናል።
ሦስት የማላደርጋቸውና አሳቤ ያልሆኑ ነገሮችን (disclaimer) ላስቀምጥ። አንደኛ፥ ደቡብ ወይም መካከለኛው ደቡብ ስል የስነ ሰብእ ወይም ስነ ሕዝብ ግምጋሜ (anthropological and demographic assessment) የማቅረብ አሳብ የለኝም። በዚያ ሕዝብ መካከል ተወልጄ ስላደግሁ በመጠኑ ያንን ማድረግ እችላለሁ። ግን ግቤ ያ አይደለም። ሁለተኛ፥ ከሕዝብ ማንነት፥ ከዘርና ጎሳ፥ ከፖለቲካ አቋም፥ ግልብ ከሆነ የሕዝብ ጅምላ ፍረጃ ጋርም ምንም ጉዳይ የለኝም። እነዚህ ነገሮች ከመንደርደሪያቸው የተሳሳቱ በመሆናቸው፥ እንኳን ለመንፈሳዊ ፋይዳ፥ ለማኅበራዊና ባሕላዊ ጉዳዮችም ግብዓት የመሆን አቅም የላቸውም። የደቡብ ሰዎች እንደዚህ ናቸው፤ የሰሜን ሰዎች እንደዚያ ናቸው የሚል አመለካከት በራሱ ከተፋልሶ የመነጨ ነው። ሦስተኛ፥ በመካከለኛው ደቡብ ሐሰተኛ ነቢያት በብዛት መውጣታቸውና ብዙዎችን ማስከተላቸው እውነት ቢሆንም፥ ይህን ስል እውነተኛ ዋጋ ከፋይና የጠሩ አማኞች መኖራቸውን በመዘንጋት አይደለም።
በመካከለኛው ደቡብ ወንጌል የሮጠበት ዘመን ነበረ። ታሪኩ ብዙ ተወስቶአል። በመከራ ውስጥ ያበበች ቤተ ክርስቲያን፥ ጠረጋ፥ የእኩለ ሌሊት ወገግታ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን፥ ኤሎሄ እና ሃሌሉያ፥ ኢትዮጵያውያን የወንጌል ጀግኖች፥ ወዘተ፥ በደቡብና መካከለኛው ደቡብ ወንጌል የዘመተባቸው ታሪኮች የተዘገቡባቸው በጣም ጥቂት የአማርኛ መጽሐፎች ናቸው። የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ወንጌል ሮጦ፥ ብዙዎች ወንጌል ሰምተው ብዙዎች አስገራሚ መዳንን ወረሱ። የመጀመሪያዎቹ የወንጌል መልእክተኞች ወደ ማዕከላዊ ደቡብ የሄዱት መንገድ ስተው ነበረ። ወደ ጂማ እየሄዱ ያሉ መስሏቸው ብዙ ከተጓዙ በኋላ መመንገድ መሳታቸውን ያወቁት የብዙ ቀናት መንገድ ተጉዘው ከምባታና ሀዲያ ከደረሱ በኋላ ነው። ከዚያ ነበር ገሚሱ እዚያ ቀርተው የቀሩት ወደ ወላይታና ወደ ሲዳማ ያቀኑት።
ወንጌል ተሰበከ፤ ጥቂቶች ዳኑ፤ ወንጌል ሰፋ ብዙዎች ዳኑ፤ ተለወጡ፤ ለውጡም ከፍተኛ ነበረ። አንዳንዱ ለውጥ ማኅበራዊ መዋቅርንም ያናጋና መልኩንም የቀየረም ነበረ። መጀመሪያ ቃሉን ሰምተው መንፈስ ቅዱስ የለወጣቸው የጥቂቶች ለውጥ ምስክር እየሆነ በብዙዎች ዘንድ ድንቅ ለውጥ ታየ። አጋንንታዊው ጭነትና ቀንበር ቀላል አልነበረምና አርነቱ ሞገስን የተላበሰ ነበረ። ወደ ክርስቶስ ሲመጡ ዓለምን፥ ሰይጣንንና ሥጋን ክጃለሁ በማለት እጅን ከፍ አድርገው እያነሡ ነበር የሚመጡት። እውነትም፥ እነዚህን ክደው ነበር የተከተሉት። እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። እውነተኛ ደቀ መዛሙርት በሉቃ፣ 9፥23 የተጻፈው ነው፤ ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።
የመጀመሪያው ትውልድ ለብዙ ውጪያዊ መከራና ስደት የተጋለጠ ነበረ። ማኅበረ ሰቡ ገሚሱ ሃይማኖታዊና ከፊሉ ጣዖት አምላኪ ነበር። ሁለቱም ወንጌላዊ ክርስትናን አሳዳጆች ሆኑ። የጣሊያን አጭር የወረራ ዓመታትም መከራውን አባሱት እንጂ አልቀነሱትም። ክርስትና ግን ውጪያዊ መከራዎች እንደሚያብሱት እንደ ሐዋርያት ዘመን ዳርና ድንበሩ ሰፋ። በጥቂት ዓመታት የአማኞች ቁጥር ከመቶዎች ወደ ሺህዎችና አሥር ሺህዎች አደገ። የጅምላና የደቦ መከተል ግን አልነበረም። ዋጋ የሚጠይቅ፥ ምንም የጥቅም ገመድ ያልተበተበው ያ ክርስትና አሁን ካለው መልክ የተለየ ነበረ። ያ ትውልድ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ፥ በመከራም እያለፈ ለተተኪው ትውልድ ወንጌልን አስተላለፈ።
ከዚያስ? ከዚያ ሁለተኛና ሦስተኛ ትውልድ መጣ። የአባቶቹን አምላክ ያላወቀ ብቻ ሳይሆን፥ የማወቅ ፍላጎት ያላደረበት። ያንን አምላክ ሳይሆን ነፋስን የሚከተል ትውልድ መጣ። ደግሞ አመጣጡ በአጭር ጊዜ ነው። ልብ ማለት ያለብን፥ ያ አካባቢ በኢትዮጵያ የሕዝብ እድገት የፍጥነት መጠን ቀዳሚው አካባቢ ነው። በብዙዎች አካባቢ እጥፍ ብቻ ይሆን የነበረው በ5 እና 6 እጥፍ ያደገ ቁጥር ነው። ቀጣዩ ትውልድ ሲባል ከ50 እና 75 ዓመታት በኋላ የመጣው አሁን በወጣትነትና በጎልማሳነት ዕድሜ ክልል የሚገኘው ማለት ነው።
የክርስትና ቁጥር ሲጨምር ጉልበቱና መሰጠቱም አብሮ አልቀጠለም። በሐዋርያት ዘመን ወንጌል እንደ ቋያ እሳት የነደደባቸው አገሮች ብዙ ነበሩ፤ በዘመናት የከሰሙ መሆናቸውም የታየ ጉዳይ ነው። እዚህም ቅርጹና ቅርፊቱ እያለ ከውስጡ ምንነቱ እየጠፋ መጣ። ክርስትና እንደ ባሕላዊ ሃይማኖት እየሆነ መጣ። ለዚህ ትውልድ ክርስቶስ የራሱ ሳይሆን የአባቶቹ አምላክ ሆነ። ደቀ መዝሙር ያልተደረገ ትውልድ አባቶቹን ተካ። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ። የሚለው ትእዛዝ ተጣለ። በኋላው ለመሄድ መውደድ፥ ራስን መካድ፥ መስቀልን መሸከም፥ ተሸክሞ ዕለት ዕለት መከተል ቀረ። በአጭሩ ደቀ መዝሙርነት ተናቀ።
ይህንን ምክንያት አንድ እለዋለሁ።
ይቀጥላል።
ዘላለም መንግሥቱ
ያዕቆብና ኤሳው
ወንድማማቾች ናቸው
በልመና የተጸነሱ ሁለት ወገኖች
መንትዮች
አንዱ
መልኩ ያማረ ፀጉር ለብሶ የተወለደ፤ ቀድሞ ከማህጸን የወጣ "ታላቅ"
ወንዳወንድ ነው ውጪ ውጪ የሚል ፤ ሻካራ እጅ ያለው ፤ አድኖ ለቤተሰቡ ምግብ የሚያመጣ በአባቱ የተወደደ ፤ ራስ ወዳድ ኩሩ የአባቱ ልጅ ፤ ከቤቱ መውጫ መግቢያ ይልቅ ሜዳ ሸንተረሩን ጫካ እና ገደሉን የሚያውቅ ፤ የምድረበዳ ሰው ፤
አንድ ቀን ራበው ፤ በአንድ ቀን ምሳ በአንድ ሳህን ምስር ወጥ ብኩርናውን ሸጠ፤ የሕይወትን ዋጋ የኑሮን ዘዬ ያቃለለ የአሁንን ጥጋብ ብቻ የሚያውቅ ፤ የምድር ቅራቅንቦ ለመሰብሰብ በየማለዳው ቀስቱን ስሎ የሚሮጥ ፤ ለብኩርና ግድ የሌለው ፣ የሰማይ ነገር የማይማርከው ፤ ዘለአለማዊ ሕይወት የማይናፍቀው፤ የከበረውን ከተዋረደው የማይለይ ፤ ጥበብ የጎደለው ጉልበት ብቻ ያደለው።
አታግባ ከተባለው ያገባ ፤ እናት አባቱን አሳዛኝ ሚስቶች ያሉት ፤ የአባቱን ትዕዛዝ የማይሰማ
ባለጸጋ ነው ግን ብኩርና የማይገባው ፤
ለቃልኪዳን ግድ የሌለው፤
400 ስራዊት ፤ ላሞች ባሪያዎች እና ጦር ያሉት ፤ ለታናሹ የተገዛ ፤ ስሙ ትውልድ የማይሻገር።
ሌላው
ጭምት የቤት ልጅ ፤ ከማእድቤት የማይጠፋ ወጥ የሚያማስል ፤ በእናቱ የተወደደ ምስር ወጥ የሚሰራ የእናቱ ልጅ ፤ ብልጣብልጥ ተንኮለኛ ፤ አባ መላ፤ ስም የሚቀይር ከቀዬው የማይርቅ ሲጠራ ቶሎ የሚደርስ ፤ ቆዳው ለስላሳ ፤ ብኩርናን የሚያውቅ ፤ መጠበቅ የሚያውቅ ፤ አሳቻ ሰዓት የሚጠብቅ ፤ በገዛ ፈቃዱ ያታለለ የዋሸ ከእናት ከአባቱ ቤት በትሩን ብቻ ይዞ የሸሸ ፤ ድንጋይ የተንተራሰ፤ከሰማይ እስከ ምድር የተዘረጋ መሰላልን በህልም ያየ ፤ የተቅበዘበዘ ሰው የናፈቀ ፤ ያለቀሰ ፤ ሰው ቤት የገባ ፤ የተገዛ የተሞኘ ፤ ብልጡ ተበለጠ ፤ አታላዩ ተታለለ ፤ 14 አመት የተገዛ ኋላም አስራ ሁለት ነገድ ሆነ ፤ በዛ ተትረፈረፈ ! በእንግድነት በለፀገ ፤ ባለሁለት ክፍል ሰራዊት ሆነ ፤ ለብቻው ቀረ ታገለ አሸነፈ ፤ ተሰበረ አነከሰ ፤ ሮጦ እንኳ የማያመልጥ ሆነ፤ግን ተባረከ ፤ ብልጠቱ እንዳላዳነው አወቀ ፤ ፊትለፊት ከአምላኩ ተያየ፤ እውነተኛ ማንነቱን አልደበቀም አሁን አልዋሸም ፤ ስሙን ጠራ ፤ አሸነፈ!
ሰጪ ሆነ ፤ ትሁት በሳል ቅድሚያ ላንተ የሚል ፤ ይቅርታ ጠያቂ ፣ ዝም ባይ ፤ ዘመኑ አጭርና ክፉ ሆኑብኝ ቢልም እድሜ ጠግቦ ፤ ልጆቹን ባርኮ በወግ ተለቅሶለት ተቀበረ ፤ እስከዛሬም ስሙ ይጠራል።
በጽጌሬዳ ጎንፋ
ወንጌላውያን አማኞች፥ በምን ታድለዋል ከተባለ፤ በነገረ-መለኮት መምሕራንና ተማሪዎች፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና በዐቃቤያነ እምነት አገልጋዮች ታድለዋል። በጣም የሚያሳዝነው ይህን የሚያውቁ፣ የሚሰሙና የሚቀበሉ አማኞች ቁጥር እምብዛም ነው። ዛሬ ላይ የሐሳውያንን ትንቢት የሚያነፈንፍ፣ ተአምርና ድንቅን የሚያሳድድ፣ ከነጠረው የወንጌል ትምሕርት ይልቅ የቧልት ሰባኬያንን መንደር የሚያጨናንቅ እንግዳ ትውልድ አድራሾችን ሞልቷል።
ወንጌል ሲሰበክ የሚያሸልቡ - ትንቢት ሲነገር የሚነቁ፤ መሠረታዊ ዶክትሪኖችን የሚንቁ - ተአምርንና ፈውስን የሚያልቁ ወገኖች ተበራክተዋል። እግዚአብሔር ግን በዘመናት ሁሉ ራሱን ያለምስክር አይተውምና፥ ዘመኑን የዋጁ መልካም ዐቃቤያነ አገልጋዮችን አስነስቷል። ሐሰትን የሚጸየፉ ለእውነት አድረው ነውርን ሁሉ በአደባባይ የሚገልጡ፣ ገቢረ-እውቀትን ገንዘብ ያደረጉ ብርቅዬ አገልጋዮችን አስነስቷል።
ይህን ዐቃቤያዊ ዘጋቢ ፈልም ባየሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔርን አመስግኛለሁ። ለእውነት እንደማደር ያለ ዕድል ለማንም የለም። ክርስቲያን የኾነ ሁሉ ይህን ዘጋቢ ፊልም እንዲያይ እመክራለሁ። ሁለቱ ምንፍቅናዎች ማለትም የእምነት ቃል እንቅስቃሴ (Word of Faith Movement) እና የብልጥግና ወንጌል (Prosperity Gospel) የተባሉት ኑፋቄች እያስከተሉት ያለውን መዘዝ በጒልህ ከማሳየት ባለፈ ብዙዎችን ያደነዘዙበትን "ወንድማዊ-ጉርብትና" መሳይ ወጥመድን በመግለጥ ኹነኛ መፍትሔዎችን እንካችሁ ይለናል።
ይህን ዘጋቢ ፈልም ያበረከታችሁልን አገልጋዮች እግዚአብሔር ይባርካችሁ። መጋቤ ስንቴ፣ ወንጌላዊ ደሉ፣ ወንጌላዊ ዳንኤል፣ ወንድም ሳሚ፣ ወንድም ቴዎድሮስ እና ሌሎች አገልጋዮች በሙሉ ጸጋ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ።
እነሆ ሊንኩ፥
https://youtu.be/Ibya_KX773s
ጵንኤል ያዕቆብ
« … የበጎች ነገር ፣ የበጎች ሀገር …»
ዘመን ተቀይሯል። እረኛው ዘምኗል። በጎቹ ግን አኹንም በግ ናቸው። እረኛው አኹን የጣልያን ሱፍ እንጂ ቁርበት አይለብስም። በጎቹ ግን ቆዳቸው ለሸላቾች ተላልፎ ተሰጥቷል። እረኛው አኹን የፈረንሳይ ሽቶ ካልኾነ አይቀባም። በጎቹ ግን ዛሬም እዳሪና ሽንታቸው ላይ ይንደባለላሉ። በረቱ ይከረፋል። እረኛው የአፉን ቅኝት ከ”ኢየሱስ" ወደ”ፍሉስ”፣ ከ”ንስሓ ግቡ” ወደ “ገንዘብ አስገቡ”ቀይሯል። በጎቹ ግን ዛሬም በግርጌው ያመሰኳሉ።
… … …
•••
እረኛው አኹን በጎቹን ከአውሬና ከነጣቂ አይታደግም። ይልቅስ የበጎቹን ሥጋ ተሻምቶ ይበላል። ሆድ ዕቃቸውን ይዘረግፋል። አጥንታቸውን ይግጣል። እረኛው ከአውሬው ከፍቷል። እረኛው ስልና ጠንካራ ጥርሶች አሉት። ይዘነጣጥላል። በቀን ይመስጋል፣ በምሽትም ያደባል። እረኛው እንደ ድሮው ትሑት አይደለም። “የእግሩን ጠፈር ልፈታ አይገባኝም” ብሎ ዝቅ አይልም። “ከመንጋው ባለቤት በላይ ነኝ” ይላል። የመንጋውን ባለቤት ይንቃል። ምንም አያይም ግን “ነቢይ” ነኝ ይላል። ወደተበተኑት አይሄድም ግን “ሐዋርያ” ነኝ ይላል። በጎቹ ግን ምንም አይሉም። ስለት በአንገታቸው ሲያልፍ እንኳ መሰማሪያቸውን አይጠረጥሩም። ሌባው እረኛው ነው። ሌባው ሊያርድ፣ ሊሰርቅና ሊያጠፋ ይመጣል።
… … …
•••
እረኝነት ከንግሥና ተሻለ። በጎችን መጠበቅ በበጎች መበልጸግ ሆነ። በጎች በተስፋ ድር ዓይናቸው ታስሯል። በጎች እግራቸው ተቆርጦ ለእረኛው መርሴዲስ ይገዛል። እረኛው አኹን መከራን አያውቅም። እጆቹ ከሀር ይለሰልሳሉ። መጽሐፉ ላይ የመከራ አንቀጾች የተዘለሉ፣ የሆድ አንቀጾች ደምቀው የተጻፉ ናቸው። እረኛው አበላሉ ዲሲፕሊን የለውም። የበጎችን ሳር የአሳሞችን አሰር ኹሉ አይንቅም። አይጠግብም። ቅኔ ያወራል። በጎች ግን አይገባቸውም። “የመስዋዕቱን በግ ጌታ ያዘጋጃል” ሲል አሜን ይላሉ። እረኛው ጥብስ ሲበላ “የማን ሥጋ ነው?” ብለው አይጠይቁም። አንዱ የሌላውን ጭራ እየተከተለ ጣፍጦ እስኪበላ ድረስ እየደለበ ይጠብቃል።
… … …
•••
በጎቹ አልተለወጡም። ላታቸው ሲመዘን ፣ ቆዳቸው ሲገፈፍ ፣ ጥርሳቸው ሲቆጠር ምክንያቱን አያውቁትም። በለመለመው መስክ ተስፋ ወደ ቄራው ይነዳሉ። ጭራሽ ለእረኛው ይሟገቱለታል። አይ የበጎች ነገር ….
…
ቢላ ሲሳል ሲሞረድ ያረግዳሉ። እሳት ሲቀጣጠል ከበው ይሞቃሉ። ስለት እያዩ አይፈረጥጡም። “ኧረ ንቁ” ያላቸውን “ቀንቶ” ነው ይላሉ። ወደ ዕረፍት ውኃ የሚመልሳቸውን ይቃወሙታል። ይልቁን ዘይትና እራፊ ጨርቅ ይማትራሉ። የመልካሙን እረኛ በትርና ምርኩዝ ይጸየፉታል። ሲጠግብ የሚንቃቸውን እረኛ «አባቴ» ይላሉ። በራሳቸው መቅኔ ወዙን ለውጦ “አመዳም” ብሎ ይሰድባቸዋል። በብዛታቸው በልጽጎ “ድሃ መንግሥተ-ሰማይ አይገባም” ይላቸዋል። በጎች ስለሆኑ ግን አይገባቸውም። እረኛው ሼክስፒርን የሚያስንቅ ጸጋዬን የሚያስከነዳ ጸሐፌ ተውኔት ነው። የሚጽፈው ድራማ ተወዳዳሪ የለውም። ነፍስ የማያስቀሩ ተዋንያን አሉት። በጎች ግን ድራማንና እውነትን ለይተው ማወቅ አይችሉም።
…
እናንተ በጎች ሆይ… ማስተዋል ይድረስላችሁ። የናቃችሁት አእምሮ ደርሶ ይታደጋችሁ። ሌላ ምን ይባላል?
ሄኖክ በቀለ
ጋሬጣው ይወገድ ...
አንድን የነበረን ሁኔታ እርሱም አስጨናቂ፣ እርሱም ሰው ሆነን ተፈጥረን የሰውነትን ነጻነት የሚነፍግ፣ እርሱም ወደ ተሰመረልን መንገድ እንዳንገባና እንዳንራመድ ጋሬጣ የሆነ፣ እርሱም ኢተፈጥሮዊ የሆነ ግን ደግሞ ተፈጥሮአዊ አድርገነው እንድንቀበለው የሚያስገድድ ... (status quo) ተቀብሎ መኖር ትህትና፣ ክርስቲያናዊ ጸባየተኛነት፣ “መስቀል ተሸካሚነት” አይደለም። አሃ! ጋሬጣ ነውና። እንዲህ ይላል ደሬ - “ጋሬጣ”ን ባነሳበት ዝማሬው፡ (ጋሬጣው ይወገድ ደርሷል የ’ኔ ተራ!)
“የንጉሱን አዋጅ - እሙን ነው መስበሬ
አምላኬን ሳልጠራ - ከቶ አታልፍም ዛሬ 3×
የሕይወት ቀጠሮን፣ የሕይወት ጉዞን ... የማይቀበል እርሱ status quoን እንደ መንፈሳዊነት የሚቆጥር አይደለምን? ነው እንጂ! “እንግዲህ በቃህ - እጅህን መልስ!” (2ኛ ሳሙ. 24፥ 16) የሚል የአምላክ አዋጅ ከሰማይ እስኪወጣ፣ አጥፊውም እጁን እስኪሰበስብ ድረስ በጸሎት የሚታገሉ ብጹዕ ናቸው። status quoን ቀያሪ ናቸው። ጥፋትንና ውድመትን፣ ሞትና መቅሰፍትን፣ ኢፍትሃዊነትንና ጭቆናን፣ ጥላቻንና ኢሰባዊነትን - ምን ማድረግ ይቻላል “የአምላክ ሥራ ዘወርዋራ” ነው ብሎ መቀበል ስንኩልነት ነው፤ አልተመረመርነውም እንጂ ስም ያለው መንፈሳዊ በሽታ ነው።
የገዘፉና የበረቱብንን ሁኔታዎች (status quoን) የሚለውጡ ሳይታክቱ ዘወትር የሚጸልዩ ብጹአን ናቸው። እግዚአብሔር የstatus quo መሣሪያዎችን - የሰይጣን ባለሟሎችን ክንድ ቄጠማ ያደርጋልና። ደግሞም ስለመበለቲቱ ፍርድ አልባነት ምክንያት የሆነውን - “እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር” ዳኛን ልቡን ያቀልጣልና።
እስቲ ቅዳሜ አብረን እንጸልይ!
ተገኝ ሙሉጌታ
ከዘላለም መንግስቱ
የተወደዳችሁ ወገኖች የጌታ ሰላም ይሁንላችሁ፤ ይብዛላችሁም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በመሥራት ላለፉት ብዙ ዓመታት ቆይቻለሁ። በተለይ ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ሙሉ ጊዜ ሰጥቼ ስሠራው ቆይቻለሁ። በጌታ ቸርነት ከ23 ዓመታት በኋላ ባለፈው ወር፥ ልክ የዛሬ ወር ተጠናቅቋል። እግዚአብሔር ይመስገን።
ይህ መዝገበ ቃላት ወደ 1350 ገጾችና ከ4ሺህ 800 ቃላት በላይ የያዘ፥ ለእያንዳንዱ ቃል ከምንጭ ቋንቋዎች አቻ ቃላትን፥ ትርጕምና ዝርዝር መፍቻ፥ እንዲሁም በቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ያካተተ ነው። ይህ ሥራ በተጠቃሚዎች ሁሉ፥ በተለይም በክርስቲያኖችና በአገልጋዮች እጅ ትልቅ እሴት የሚሆን መጽሐፍ ነው።
በኢትዮጵያ ይህን ሥራ ለማሳተም የእናንተ እርዳታ አስፈልጎኛል፤ ለጋስ እጃችሁንና ቸርነታችሁን እጠይቃለሁ። የgofundme አካውንቱ ሊንክ ይህ ነው፤ https://gofund.me/2c4353f8
እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ ለበረከትም ያድርጋችሁ።
ዘላለም ነኝ።
Hello my friends. May the peace of Christ be on you. I have been working on the Amharic Bible Dictionary (ABD). The last few years were entirely dedicated to this prodigious work. It came to completion last month (exactly a month ago) after 23 years. Praise God.
The ABD is a 1350 plus pages work with over 4800 entries complete with source language equivalents, meanings, extensive definitions as well as ample Bible verse references. This work would be an asset in the hands of all users; especially Christians and ministers.
To have it printed in Ethiopia I need support, and here I am asking for your helping hands and generosity. The gofundme account link is: https://gofund.me/2c4353f8
God bless you and make you a blessing.
Zelalem Mengistu
በወንጌላዊው ክርስትና ውስጥ አሁን እየተከሰተ ያለው ነገር ልክ በ፪ኛ ጴጥ 2፥1-3 ላይ እንደተጻፈው አይነት ነው።
ምን አይነት?
***
ሐሰተኞች ነቢያት በሕዝቡ መካከል እንደ ነበሩ፣ እንዲሁም በእናንተ መካከል ሐሰተኞች መምህራን ይነሣሉ፤ እነርሱም [ሐሰተኛ መምህራን/ነቢያት]
1 - የዋጃቸውን ጌታ እንኳ #ይክዳሉ
2 - ጥፋት የሚያስከትል የስሕተት ትምህርት #በስውር ያስገባሉ
3 - በዚህም በራሳቸው ላይ ድንገተኛ #ጥፋት ያመጣሉ
4 - ብዙዎች #አስነዋሪ ድርጊቶቻቸውን ይከተላሉ
5 - በእነርሱም ምክንያት የእውነት መንገድ #ይሰደባል
6 - እየተስገበገቡ #በፈጠራ ታሪካቸው ይበዘብዟችኋል
7 - #ፍርዳቸው ከጥንት ጀምሮ ዝግጁ ነው፤ መጥፊያቸውም አያንቀላፋም።
***
ባለፉት ጥቂት ዐሥርት ዐመታት በሐሰተኛ ነቢያት/መምህራን ብዙ ድብልቅልቅ ነገሮች በወንጌላዊው ክርስትና ውስጥ ተከስተዋል፥ እየተከሰቱም ነው። በስውር ሰርጎ የገባው "የኮንትሮባንድ ክርስትና" ከእውነት መንገድ ጋር ስለተቀላቀለ ብዙዎችን አስቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜም እውነታው ሳይቀየር ልዩነቱ ግን እየደበዘዘ መጥቷል። ስለዚህም እነዚህን በውል ለመለየት "#ደማቅ_መስመር" ያስፈልገናል ይለናል ዘጋቢ ፊልሙ!
እንዴት መለየት ይቻላል? ቤተ ክርስቲያን በታሪክ እንደዚህ ሲገጥማት ምን እርምጃ ወሰደች? ውጤቱስ ምን ነበር? የሚሉ ጥያቄዎችን ዘጋቢ ፊልሙ በግልፅ ይመልሳል። ለግል ውሳኔም ሆነ የሚሰሙንን ለመታደግ የሚረዱ ወሳኝ መልዕክቶች ተዳሰዋል። እንድትመለከቱት ጋብዘናል!
ጠቃሚ መስሎ ከታያችሁ ለሌሎችም እያጋራችሁ ይሁን!
#ሰርጎ_ገቡ_ትምህርት
#ደማቅ_መስመር_ያሻናል
መልካም ሳምንት! 👋👇
https://youtu.be/Ibya_KX773s
ፍጹማን ግርማ
መልሰህ አብጀን!
የአሦር ዓለም ዐቀፍ አገዛዛ ባበቢሎን መነሣት መሰርሰር በጀመረበት ጊዜ፣ ይሁዳ (የደቡቡ ክፍል) በጥልቅ መንፈሳዊ ቀውስ ውሰጥ ነበር። የታሪክን ፍሰት፣ የነገሥታትን መነሳትና መውደቅ በሉዓላዊነቱ የሚቆጣጠር ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር፣ እስራኤል (የሰሜኑ ክፍል) ቃል ኪዳኗን በማፍረስ በኀጢአት መንገድ በመጽናቷ፣ በ 722 ዓ.ቅ.ክ ለአሦር አሳላፎ ሰጣት። የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስና በወቅቱ የነበሩት መሪዎች፣ ከእስራኤል አልተማሩም። ይልቁንም ልባቸው ከንስሓ እጅግ በራቀ መልኩ ደንድኖ ነበር።
“ለከዳተኛ ዪቱ እስራኤል ስለ ምንዝርናዋ ሁሉ የፍች ወረቀቷን ሰጥቼ አባረርኋት። ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አይታ እንዳልፈራች አየሁ፤ ወጥታም አመነዘረች። በቅሌቷም ምድሪቱን አረከሰች፤ ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳ ወደ እኔ የተመለሰችው በማስመሰል እንጂ በሙሉ ልቧ አልነበረም” ይላል እግዚአብሔር። (ኤር. 3: 8-10)
ይሁዳ በአመራር፣ በመንፈሳዊ፣ በሞራል፣ በሥነ ምግባርና በፍትሕ ማጕድል ዝቅጠት ውስጥ ገብታ ነበር። ፈረሓ እግዚአብሔር እንደ ራቃት የእግዚአብሔርም ክብር እንደ ሸሻት አታስተውልም ነበር።
የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች፤ ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ? (ኤር 5፥30-31)።
ይህ ውደቀት በአንድ ጊዜ የሆነ አይደለም። ሥር የሰደደና የቈየ መንፈሳዊ ሕመም ነበር። ቀደም ሲል በሚክያስ በኩል እግዚአብሔር ሐዘኑን ገልጦ ነበር። “አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፥ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ።” (ሚክ. 3፥11)።
እግዚአብሔር ይሁዳን በ 586 ዓ.ቅ.ክ አካባቢ ለባቢሎን መንግሥት አስከፈ የ 70 ዓመት ግዞት አሳልፎ ሰጠ። የመጨረሻው ንጉሥ ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየ ባቢሎናውያን ልጆቹን ገደሉበት፤ ሁለት ዐይኖቹንም በማውጣት በሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። የእሥራኤል ውበት የነበረውና በአንድ ወቅት ካህናት ማገልገል እስኪሳናቸው ድረሰ የእግዚአብሔርን ሀልዎት ያስተናገደው ቤተ መቅደስ፣ እንዲሁም ክብራቸው የነበረቸው ኢየሩሳሌም በእሳት ጋዩ፤ ቅጥሯቸውም ፈረሰ- ክብር ከእስራኤል ላይ ሸሸ።
የኤርምያስ ሰቆቃ፣ የኢየሩሳሌምን ዐመፅ፣ ውርደት፣ እፍረት፣ ስብራትና ሐዘን ይገልጣል።
“እግዚአብሔር መሠዊያውን ናቀ፤ መቅደሱንም ተወ፤ የቤተ መንግሥቶቿን ቅጥሮች፣ ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤. . . ዐይኔ በለቅሶ ደከመ፤ ነፍሴ በውስጤ ተሠቃየች፤ ልቤም በሐዘን ፈሰሰች።” (ሰቆ. 2፥7-11)።
ይሁን እንጂ፣ የግዞት ቅጣቱ ከተሐድሶ ተስፋ ጋር ነበር። “በሸክላ ሠሪው” የቀረበው ተምሳሌ ይህንን ያሳየናል። ምንም እንኳን ይሁዳ “ተሐድሶ ተስፋ” ማድረግ በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ራሷን ብታገኝም የእግዚአብሔር ፍርድና ምሕረት አልተለያዩም ነበር። ቅጣት አለ፤ ይሁዳ በጨካኙ ባቢሎን እጅ ትሰባበራለች፤ ትበታተናለች። ሆኖም እንደገና ትሠራላች። እግዚአብሔር በልዕለ ኀያልነቱ የቅጣቱ መሳሪያ የነበረውን ባቢሎንን፣ እንዲሁም ብዙ ነገር የተበላሸባትንና በቁጣው ሥር የወደቀችውን ይሁዳን በአንድ ጊዜ በእጁ ይዟል። በሌላ አባባል፣ በአንድ እጁ ፍርድ በሌላኛው ደግሞ ምሕረትን ይዟል። በቅጣትና በስብራት መካከል፣ የተሐድሶ ተስፋ ነበር።
“ከጭቃ ይሠራው የነበረውም ሸክላ በእጁ ላይ ተበላሸ፤ ሸክላ ሠሪውም በሚፈልገው ሌላ ቅርጽ መልሶ አበጀው።” (ኤር. 18፥5)።
በሸክላ ሠሪው እጅ የተከናወነው ሥራ፣ በዘፍጠረት ላይ እግዚአብሔር በፈጣሪነትና በፍጥረት አዳሽነት ራሱን የገለጠበትን ታሪክ ያስታውሰናል። እግዚአብሔር ለህልውናው ሰበብ የሌለው የፍጥረነት ብቸኛ መገኛ ነው። ያለ እርሱ ፍጥረትና ታሪክ ትርጕም የላቸውም። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ. 1፥1)። ሰውን ጨምሮ፣ በዐይን የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረው ራሱ እግዚአብሔር ነው። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።” (ዘፍ. 1፥1)፤ “እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍ. 2፥7)።
በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንደምናየው፣“እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” (1÷31)። ይህን እጅግ መልካምነት፣ ሰላም [ሻሎም]፣ እረፍት እንዲሁም በሁሉ ረገድ እግዚአብሔር በመግቦቱ ለፍጥረት ሁሉ የሰጠውን ምሉዕነትና ስምረት ያበላሸው ኀጢአት ነው። አዳምና ሔዋን፣ በእግዚአብሔር ላይ ዐመፁ። የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ሆነው ሳሉ “እንደ እግዚአብሔር ለመሆን” በመፈለግ ከንቱ ምኞትና ባለመታዝዝ በደሉ።
በኀጢአት ምክንያት፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድና ሁለት ላይ የነበረው የፍጥረት ስምረት፣ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሊያስታካክለው በማይችለው መልኩ ከሥር፣ ከመሠረቱ ተናውጧል። ሆኖም ሰው ከእግዚአብሔር ምሕረት፣ ተስፋና ተሐድሶ ውጭ አልወደቀም። ከዘፍጥረት ሦስት እስከ ራእይ የምንመለከተው ይህንኑ የእግዚአብሔርን የትድግና ሥራ ነው። አምላክ ሥጋ ኾነ! ክርስቶስ መሰቅል ላይ ደቀቀ፤ በእግዚአብሔርና በሰው፤ በሰውና በሰው፤ በፍጥረትና በሰው መካከል የተበላሸውን ግንኙነት ሁሉ አደሰ!
ሸክላ ሠሪው የተበላሸውን ሸክላ መልሶ ማበጀቱ ይህንን እውነት ያሳየናል። ሸካላው ተበላሸ፤ ሆኖም ብልሽቱ ከሸክላ ሠሪው መልሶ የማበጀት ፈቃድና ዐቅም በላይ አልነበረም። መልሶ የመበጀቱ ተስፋ በሸክላ ሠሪው እጅ ብቻ ነበር። ልክ እንደዚሁ፣ ብዙ ነገር ለተበላሸበት ሕዝቡ እግዚአብሔር የተሐድሶ ተስፋ ይሰጣል፦ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ጭቃው በሸክላ ሠሪው እጅ እንዳለ፣ እናንተም እንዲሁ በእጄ ውስጥ ናችሁ።” (ኤር. 18:6)። የሸክላው ታሪክ አላበቃም፤ አልተዘጋምም። የእግዚአብሔር ሕዝብም ታሪክ ልክ እንዲሁ ነበር። “የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ (ኤር 31፡4)።
እኛም እንደ አገር ብዙ ነገር ተበላሽቶብናል። ፈርጀ ብዙ በሆነ መንፈሳዊ ቀውስ ውስጥ አለን። እንደ ግለሰብና እንደ ቤተ ሰብ ደግሞ መልካቸውና መጠናቸው ይለያዩ እንጂ የእግዚአብሔርን የተሐድሶ እጅ የሚሹ የተበላሹ ነገሮች ይኖሩናል። እኛ በእውነት እንመለስ እንጂ፣ እግዚአብሔር የሚያድስ አምላክ ነው። ሆኖም እኛም ድርሻ አለን፡ “ስለዚህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ተግባራችሁን አቅኑ።” (ኤር. 18፥11)። ውድቀታችንን ካልተረዳንና ተሐድሶ እንደሚያስፈልገና ካላመንን፣ ተሐድሶ አይሆንም። መታመሙን ያልተቀበለ በሽተኛ፣ እንዴት ፈውስ ይገኝለታል?
“በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ? ማንም እንዲሞት አልሻምና፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ!" (ሕዝ. 18፥31-32)።
ዘመን በየሠፈሩ ቢለወጥ እኔ ምን ቸገረኝ? ግን…
በኢትዮጵያ ደቡባዊ ክፍል የክርስትና እምነት ከመግባቱ በፊት በወላይታ አካባቢ “ጦሳ” የሚባል አምላክ ነበር። ዙማ ጦሳ (የተራራ አምላክ)፥ ሳሎ ጦሳ (የሰማይ አምላክ)፥ አባ ኡማ ጦሳ (የሃይቅ የወንዝ አምላክ)፥ እየተባለ ይጠራ “መሬት ከዬት መጣች?… ጸሐይና ጨረቃን ማን ፈጠራቸው?… ሰዎች ሲሞቱ ወዴት ይሄዳሉ?… ሌሎችንም ጥያቄዎች ለመመለስ ሲሉ በምናባቸው የፈጠሯቸው አማልክት ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ። ይህ “ጦሳ” በራሱ አምሳል ሰዎችን የፈጠረ አንድ ሉዓላዊ አምላክ አይደለም። በየመንደሩ በተለያየ ይዘትና ቅርጽ በተለያየ ሥርዓት የሚመለኩ አማልክትን የሚያመለክት ነው። ሰውን ከምድር አፈር ያበጀው የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር፥ የክርስቶስ አባት የሆነው የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር፣ ለሰው ልጆች ኃጢአት ልጁን አሳልፎ የሰጠው የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር፥ መንፈሱን ለአማኞቹ የሰጠው የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር አይታወቅም ነበር።
ዳሞታ አንታሺያ፥ ቃይዳራ፥ ሙሉጉሻ፥ ክቶሳ የሚባሉ ጥቃቅንና አነስተኛ አማልክትም ነበሩ። በየመንደሩ በየቤቱም አምልኮ ለነዚህ ጌቶች ይሰጥ ነበር። ጠንቋዮች፥ ዕድል ተናጋሪዎች፥ ጦር መሪ አማካሪዎች፥ ቃሊቻዎች ነበሩ። ሰዎች ዓመት በዓላት ሲደርሱ ያርዱላቸዋል፥ ዘግነው ይበትኑላቸዋል፥ ሞልተው ያፈስሱላቸዋል። የኦርቶዶክስ ክርስትና ከወንጌላውያኑ ክርስትና ቀድሞ ወደ አካባቢው የመጣ ቢሆንም በሁለት ምክንያቶች ብዙም ሕዝቡን ከነበረበት የአማልክት ፍርሃትና እሥራት ከሠይጣን ግዞት ሊያላቅቅ አልቻለም ነበር። አንደኛው ምክንያት:- የተዋሕዶ አገልጋዮች ለራሳቸውም ደብተራነትን፥ አስማተኝነትን፥ ሞራ ገላጭነትን፥ መተተኝነትን የሚለማመዱ በመሆናቸው የወንጌል አቅም አልነበራቸውም። ሁለተኛው:- የተዋሕዶ ክርስትና በገዢዎች በኩል አድርጎ የመጣ የቤተ መንግሥት ኃይማኖት በመሆኑ ጨቋኝና አስገባሪ ሕዝቡን ጭሰኛ የሚያደርግ ነበር እንጂ የነፍስና የመንፈስ አገልጋይ ኃጢአተኛውን ከአዳኙ ጋር የሚያገናኝ ለጥያቄው ምላሽ የሚሰጥ ሸክሙን የሚያቀልልለት አልነበረም።
የወንጌል መልዕክተኞች ከምዕራቡ ዓለም ትምህርትና ሕክምናን እንደ መግባቢያ ቋንቋ ይዘው ሲመጡ ሕዝቡ የተዋሕዶን ክርስትና ከዳር እስከዳር ቢቀበልም ሙሉ ልቡን ያልሰጠበት የቀድሞ አማልክቶቹንም ሳይጥል ደርቦ ይዞ ለይስሙላ ክርስትና ተነስቶ ስሙን በክርስትና ስም አስቀይሮ መስሎ የሚኖርበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። በሚስዮናውያኑ የወንጌል ስብከት የክርስቶስን ወንጌል በትክክል ሲሰሙ ፈጣን ምላሽ በመስጠት በአጭር ጊዜ ሊባል በሚችል ሁኔታ የወንጌል አማኞች ክርስትና ወላይታንና አካባቢውን እንደ ሰደድ እሳት ተዳረሰ። አንዳንድ ጸሐፊዎች ስለዚህ የወንጌል ሥርጭት ሁኔታ ሲናገሩ “fire on the mountain” ብለዋል። በወላይትኛ “ጠረጋ” ተብሏል። የኦርቶዶክስ እምነት ከባላባቶችና ከአስገባሪዎች ጋር ባላቸው ጥምረት ስደትና መከራ ያደረሱባቸው ቢሆንም ያኔ ጌታን እንደ ግላቸው መድኃኒት የተቀበሉ ሰዎች ስደቱን ሳይፈሩ እየታሰሩም እየተገረፉም ጸንተው የወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያናት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በአካባቢው በፍጥነት ተስፋፍቶአል። ወንዲዬ አሊ ለቤተ ኢርስቲያን ታሪክ መጽሐፉ “በመከራ ውስጥ ያበበች ቤተ ክርስቲያን” ያለው ከዚህ መነሻነት ይመስለኛል።
የወላይታ አካባቢ እንደ ማንኛውም ሌላ ግዛት ሁሉ የራሱ አስተዳደራዊ መዋቅር፥ የራሱ አካባቢ በቀል የቀንና የዘመን አቆጣጠር፥ የራሱ አካባቢ በቀል የገንዘብ ልውውጥ ሥርዓት የነበረው ሕዝብ መሆኑን ማንም የሚክደው አይደለም። የገንዘቡ መጠሪያ “ማርጮ” ይባል እንደነበር ሰምቻለሁ። የወላይታ ማኅበረሰብ እንግዲህ የራሱ ቀደምት የአምልኮ ሥርዓት፥ የአኗኗር ወግ፥ የቋንቋና የባሕል ሁኔታ፥ የተለያዩ በዓሎችና የአከባበር ሥርዓቶች ነበሩት። አዲስ ከመጣው ዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት ጋር ባለመጣጣማቸው ምክንያት በዋናነት አዲስ ከሰሙት የወንጌል ስብከት ከተቀበሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሴቶች ጋር አብረው የማይሄዱ ከመሆናቸው የተነሳ አብዛኛዎቹን ልማዶች የወላይታ ሕዝብ ጥሎአቸዋል ቀብሮአቸዋልም። አንዳንዶቹ ም ልማዶችና ሥርዓቶች ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ሰይጣናዊ ከመሆናቸው የተነሳ በክርስቲያኖች ዘንድ በገሃድ የተወገዙ ሆነዋል። “ጊፋታ” የተባለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፖለቲከኞቹ ሲያቀነቅኑ የሚሰማው የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል በተለያዩ ክርስቲያናዊ እሴቶችን ከሚንዱ ተግባሮቹ የተነሳ በወንጌላውያኑ ዘንድ ከተወገዙት ልማዶች አንዱ ነው። በርግጥ ወንጌላውያኑ “ማስቃላ” የተባለውን ክብረ በዓልንም ሆነ “ጥንቃታ” የተባለውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዓላትን እንዳያከብሩ ተደርጎአል።
የኢህአደግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ካመጣቸው ለውጦች ዋነኛው ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ቋንቋ እንዲያሳድጉ፥ የራሳቸውን ባሕል እንዲያስተዋውቁ፥ ራሳቸውን በራሳቸው ሰዎች እንዲመሩ፥ የራሳቸውን መሬትና ጥሪት ራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፥ ራሳቸውን ከሀገር ቢፈልጉ እስኪገነጥሉ ድረስ ነጻ እንዲሆኑ የማስቻል አዋጅ በሕገ መንግሥቱ ማጽደቅ ነበር። ይህ በኔ ግምት ሀገሪቱን አንድ ባደረገው የኦርቶዶክስ ክርስትና አሻራ ላይ በፕሮቴስታንት ዕምነትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልምምድ ላይ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ያስከተለ ብሔር ብሔረሰቦችን ለየራሳቸው ልዩ ልዩ አመለካከትና ልምድ ወደ ኋላ የመለሰ ተግባር ሆነ። ይህ ሥርዓት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር አንድ ያደረጉ የጋራ እሴቶችን በማውደም ሁሉንም ወደ ቀደመው ልማዳዊ ድርጊትና አሠራር መመለሱ ሀገሪቱን ቀድሞ ይገዙ ከነበሩት አጼዎች ጋር፥ የአጼዎችን ሥርዓት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ከተቀበሉት ኃይማኖተኞችም ጋር ጭምር ጥላቻንና ቂመኝነትን ያተረፈ መሆኑ ተዝቆ ወደማያልቅ አዛባ ውስጥ ሀገሪቱን አስገብቶአል። የአማራና አማርኛ ጠልነትን ጨምሮ በርካታ መራራ ዘር በትውልዱ ልብ ዘርቶአል።
ሀገርን አንድ አድርገው ከነበሩት ነገሮች አንዱ የዘመን መለወጫ ነበር። ሶላር ካላንደር የሚሉት “የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር” ባሁኑ ጊዜ በአብዛኛው በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ዘንድ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የሀገራችንም ዘመን መለወጫ ሆኖ አንድ ላይ ዘመን ስንቆጥር እንደኖርን የሚታወቅ ነው። ነበር ልበል እንጂ። አብዛኛው የዓለማችን ክፍል ደግሞ “የግሪጎሪያንን ዘመን አቆጣጠር” ይጠቀማል። ዘመን መለወጫ የራሱን ቀመርና ስያሜ አግኝቶ የራሱንም ታሪካዊ አመጣጥ ተከትሎ የመጣ ነው። BC (Before Christ) በተለምዶ ዓ.ክ.ል.በ (ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት የምንለው) & AD (Anno Domini) በላቲን የጌታ ዓመት የተባለው ዓመተ ምህረት ብለን ስንጠራው። ወደዚያ ዝርዝር አሁን አልገባም። ወደተነሳሁበት ነገር ስመለስ ግን የተለያዩ ብሔረሰቦችና ጎሣዎች የየራሳቸው የዘመን አቆጣጠር ቀመር እንዲከተሉ መነሻው ወደማይታወቅ ልማዳዊ ዘመን መለወጫ አቆጣጠርና ልማድ መመለስ በሀገራችን ሁኔታ የግድ ሆነ። ለምሳሌ ወላይታ “ጊፋታ” የተባለ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ሲዳማ “ፊቼ ጫምባላላ፥ ካምባታ “ማሳላ”፥ ኦሮሞ “እሬቻ”፥ ሐዲያ “ያሆዴ” ፥ የአማራ እንቁጣጣሽ እና ሌሎችም እንደዚያው “እኛም የኛ አለን” ወደሚሉት አቆጣጠሮች ዘወር አሉ። ሁላቸውም የየራሳቸው አምልኮአዊ ልማዶችን አቅፎአል።
ዝም ብለህ ስታስተውል — የአዕምሮ ጤና እጦትን ሲበዛ ኖርማላይዝድ አድርገነው ቆይተን ህሙማን ከነሕመማቸው አልጋቸውን ይዘው ወደ አደባባይ ወጥተው ጤነኞችን ሲመሩ ታይና —አጃኢብ ትላለህ።
ታዲያ ነገሩን ስንቃወም ራሱ ግብሩን ከዓለማዊና መንፈሳዊ የሞራል ህጎች አንፃር ብቻ በመሆኑ፤ ሁነቶቹ እየተደጋገሙ መከሰታቸውን ቀጥለዋል።
ጥቂት ከሐይማኖት ጋር ተያያዥ የሆኑ መታከም የሚችሉ የአዕምሮ ህመሞችን ላስታውስህና በገዛ ልቡናህ አካባቢህን አስተውል— ያዝ!
① Religious Schizophrenia —
የስትሶፈርኒያ አንደኛው መልክ ሆኖ የዚህ ዲስኦርደር ያለበት ግለሰብ ያለ ምንም ተጨባጭ እውነታ ከሰማያዊ አካል ጋር የተጋነነ ቅርርብ ያለው፤ ከፈጣሪው ጋር የሚነጋገር ፤ ከሌላው ተለይቶ የተቀባና በፈጣሪው የተመረጠ መንፈሳዊ ሰብዕና፤ ነብይ ወይም መሲኅ ሆኖ የሚሰማው ሊሆን ይችላል። የህመሙ ችግር ይሄ ብቻ አይደለም፤ በገዛ ቅዠትህ ጥቂት የማይባሉ ቡድኖችን ለመዘወር ስትሞክርና ከሐሳብህ የሚያፈነግጡትን ማውገዝ፣ ማንኳሰስ ብሎም ማጥቃት ስለሚወሰውስህ ጭምር ነው።
② Religious Trauma Syndrome (RTS)—
በተበታተነ ሀሳብ ውስጥ ሆነህ በአንድ ሐይማኖት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ትቆያለህ፤ በቆይታህ በራስህ ምክኒያትና ምርጫ በምትወስደው እርምጃ ወይም በሌሎች በሚደርስብህ ጫና በሐይማኖቱ አባላት ውግዘት፣ መገለል፣ ወዘተ ይደርስብሀል። በኋላ በአንዳች ምክኒያት ሐይማኖት ትቀይራለህ። ሕይወትህን ሙሉ ዴዲኬትድ የሆንክለትን ሐይማኖት ትተህ መውጣቱም ሆነ በዚያ የገጠመህ ነገር ላይ አይሆንምና Trauma ያጋጥምሀል። ንዴት፣ ቁጭት፣ ተቀባይነት የማጣት ስጋት፣ ሐፍረት ያሰቃዩሀል። ምርጫህ ደስተኛ ሆኖ ለመታየት መሞከርና የወጣህበትን የእምነት ህብረት ረብየለሽ እንደሆነ ለማሳየት መጣር ብቻ ይሆናል— ካልታከምከው።
③ Hyperreligiosity —
ይህ የልቡና መረበሽ ከገጠመህ ጤነኛ ባልሆነ መንገድ ለገዛ ሐይማኖትህም ሆነ ሌሎች ለሚያራምዱት እምነት በእጅጉ መብሰልሰል እጣህ ይሆናል። መብሰልሰል እንዲ ቀላል እንዳይመስልህ —የቀን ተቀን ግብርህን እና ማህበራዊ ሕይወትህን መብሰልሰልህ እስኪያውከው ድረስ ምልክቶች፤ ድብቅ አጀንዳዎች፣ ሴራዎች ወዘተ መተንተን 24/7 የምታደርገው ስራ ይሆናል። ከፍ ሲልም ጥርጣሬ እና መላ ምቶችህ በገዛ ራስህ ላይ እየተደረጉ እንደሆኑ ሊሰማህ ይችላል— ካልታከምከው።
———
ተቀበልከውም አልተቀበልከውም— የዚህ የደረስንበት ዘመን ዋነኛ ስጋት የአዕምሮ ጤና ነው። የችግሮቻችን ምንጭ ከአብላጫ በላይ የሚሆኑት ልቡናዊ መንሥኤዎች አሏቸው— የግለሰብ እና የቡድን ሥነልቡና ችግሮች። እንዲያ ነው።
-------
[📷 Random}
ሱራፌል አየለ
የመከራ ስነ መለኮት
ክርስትና የቅምጥልነት፥ የድሎትና የምቾት፥ የመንፈላሰስና የመንደላቀቅ መሆኑ በሚነገርበት፥ መንገዱ ወጣ ገባ ሳይሆን የቁልቁለትና የአልጋ ባልጋ እንደሆነ በሚነገረን አሳች ዘመን ላይ ስላለን፥ ‘የአንታመምም’ አስተምህሮ እና ብንታመም፥ ‘ፈውስ ቅጽበታዊ መብታችን ብቻ ሳይሆን ሥልጣናችን ነው’ ዘመን ላይ ስላለን መከራን እንዳለ አንቆጥረውም። መከራን ለመሸሽ የምናደርገው ሩጫ፥ ሩጫው ራሱ አደናቅፎ የጣላቸው ብዙዎች ናቸው።
እግዚአብሔር ስለሚወድደን መከራን ወደ ሕይወታችን አያመጣም፤ ክርስቲያን መከራ፥ ለምሳሌ ሕመም አያገኘውም፤ አንድ ክርስቲያን ከታመመ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ጎዶሎነት፥ በእምነት ማጣት፥ በኃጢአት፥ አሥራት ባለመስጠት፥ ወዘተ፥ ምክንያት ነው፤ ይህ ከደረሰብን አጥፍተን እየተቀጣን ነው ማለት ነው፤ ጤናማ ክርስትና ከመከራ የጸዳ ነው፤ መከራ ካለበት ክርስትናው ልክ አይደለም፤ ወዘተ፥ እያሉ የሚያስተምሩና በዚህም ብዙዎችን የሚጎዱ አስተማሪዎች አሉ።
መጀመሪያ ስለ መከራ ስነ መለኮት ያነበብኩት የፊሊፕ ያንሲን፥ Where is God When it Hurts መጽሐፍ ያነበብኩ ጊዜ ነበር። አዲስ ወንጌላዊ ሳለሁ ያለ እረፍት አገለግል ዘንድ ግዴታ ውስጥ አስገብቼ ራሴን ጎዳሁና ታምሜ ሳገግም ነበር ያነበብኩት። ከዚያ በኋላ 1ኛ ጴጥሮስን እና የፊልጵስዩስን መልእክቶች ሳስተምር ይህንን እውነት ፊት ለፊት ተጋፈጥሁት። ለራስ መረዳት አንድ ነገር ነው፤ ለሌሎች ማካፈል ደግሞ ኃላፊነትን ይጠይቃል። ከሁለቱም አንድ አንድ ጥቅስ ላካፍል፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ ፊል. 1፥29። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። 1ጴጥ. 2፥21።
መከራ፥ ስቃይ፥ ስደት፥ ጭንቅና ፈተና በዚህች ምድር እና በዚህ ሕይወት ስንኖር የክርስትናችን አንድ አካል ነው። ምንም መከራና ስቃይ ገጥሞን የማናውቅ ከኖርን እናመስግን፤ ደግሞም ሊገጥመን ይችላልና ሲገጥመን እንደ እንግዳ ነገር አንቁጠረው። ከላይ ከፊልጵስዩስ እና ከጴጥሮስ እንደተጠቀሰው ቃል መከራ የከበረ ጥሪያችንም ነው። ለመዳን ብቻ ሳይሆን በመዳናችን መከራን ልንቀበልም ተጠርተናል። የክርስቶስን ፍለጋ ለመከተል ተጠርተናል። ምሳሌ ትቶልናል፤ ያም መከራ ነው። ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 1ጴጥ. 1፥6-7። ይህ መልእክት የተጻፈው ለተበተኑ መጻተኞች ወይም ስደተኞች ለሆኑ ክርስቲያኖች ነው።
እግዚአብሔርን መምሰል፥ ክርስቶስን መምሰል የተጠራንበት መጠራት ነው፤ ሮሜ 8፥29፤ 1ጢሞ. 6፥4-11፤ 2ጴጥ. 1፥6። እርሱን መምሰል ደግሞ የሚጠይቀው ዋጋ አለ፤ ዝም ብሎ መምሰል የለም፤ በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። 2ጢሞ. 3፥12።
ጳውሎስ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ ያለው እየተቀማጠለ በመኖር አይደለም። በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ 2ቆሮ. 6፥6-8።
ይቀጥላል፤
ዘላለም ነኝ።
“ካለፈው የማይማሩ፣ ይደግሙት ዘንድ ተፈርዶባቸዋል” - ጆርጅ ሳንታያና
“ሰዎች ቢውድቁ፣ እንደ ገና ከወደቁበት አይነሡምን? ሰው ተሳስቶ ወደ ኋላ ቢሄድ፣ ከስሕተቱ አይመለስምን? ታዲያ፣ ይህ ሕዝብ ለምን ፊቱን አዙሮ ወደ ኋላ ይሄዳል? ለምንስ ኢየሩሳሌም ዘወትር ወደ ኋላ ትመለሳለች? ተንኰልን የሙጥኝ ብለው ይዘዋል፤ ሊመለሱም ፈቃደኛ አይደሉም።” (ኤር. 8፥3-5)
እግዚአብሔር የይሁዳን ልበ ደንዳናነትና ያንኑ ያከሰራትን የጥፋት ጐዳና በተደጋጋሚ ለመሄድ መወሰኗን የገለጠበት መንገድ፣ እንደ አገር የእስከ አሁኑን አካሄዳችንን የሚያሳይ ይመስለኛል። ይሁዳ ያለፈው የእሥራኤል ታሪክ ያለመማሯ ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በከፋ መልኩ በመድገሟም አዝኗል። “ከከሓዲዋ ይሁዳ ይልቅ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ጻድቅ ሆና ተገኘች።” (ኤር. 3፥11)። ልክ እንደ እስራኤል፣ የአመራር፣ የመንፈሳዊ፣ የፍትሕና የሞራል ቀውስ፣ ይሁዳንም ለራስ ጥፋት አሳልፎ ሰጥቷታል።
በዚህ ዘመን ያለነው እኛም፣ ከትናንቱ መማር ተስኖናል። “ከታሪክ የማይማሩ፣ ስሕተትን ይደግሙት ዘንድ ተኰንነዋል” የሚለው አባባል እኛ ላይ ደርሷል። ከታሪክ የተማርነው ከታሪክ አለመማራችንን ነው” የተሰኘው ሌላው ሸንቋጭ አባባልም የሚያስተጋባው ይኸን መሰሉን ስንፍናችንን ይመስለኛል። አዎ፥ ከትናንቱ የማይማር ሰው በርግጥም መልሶ እንዲሳሳት ቢፈረድበት እንጂ ሌላ ምን ምክንያት ይኖረዋል? በሚዘገንን መልኩ ታሪክ ራሱን የሚደግመውና የሚደጋግመው ለዚያ ሳይኾን አይቀርም። እኛን የሚተካው ትውልድ ደግሞ፣ ከእኛ ባለመማር የከፋ እንዳያደርግ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱና ምሕረቱ ያስበን። እንደ እውነቱ፣ ለእኛም ለመመለስ ጊዜው አልረፈደም።
እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ላይ ቅኝ አገዛዝን በመቃወም ሲታገሉ የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት “የነጻ አውጪዎች” እንቅስቃሴ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ በምዕራቡ ዓለም ትልቅ ድጋፍ አግኝቶ ነበር። ይህንን የዓለም የፓለቲካ ለውጥ በወቅቱ "የእግዚአብሔር ጣት" በማለት ድጋፍ የሰጡ በርካታ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አባል አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ።
በወቅቱ ልቅ ነገር መለኮትን ያራምዱ የነበሩ መሪዎችም፣ “ድነትን” ከፓለቲካዊና ማኅበራዊ ዐርነት ጋር በማያያዝ፣ ከቅኝ አገዛዝ ዐርነት ለማግኘት ይደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን መንፈሳዊ አልባሳት ለመስጠት ሙከራ አደርገው ነበር። እንዲያውም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በባንግኮክ-ታይላንድ፣ “ድነት ዛሬ” በሚል መሪ ዐሳብ አካሂዶት የነበረው ስብሰባ በዚህ ዕሳቤ የተቃኘ፣ ኢምፔሪያሊዝምን ያወገዘና ቅኝ አገዛዝን የኰነነበት መርሐ ግብር ነበር። ሲቆይ ግን “ነጻ አውጪዎቹ” አንገት በሚያሰደፋ መልኩ ከቀደሙት ቅኝ ገዢዎች ይልቅ ከፍተው ተገኙ። መንፈቅለ መንግሥትን መደበኛ የፓለቲካ ሽግግር በማድረግ አፍሪካ ላለፉት ስድሳ ዓመታታ ፈተኛ ናት። ኾኖም በየትኛውም መልኩ ቅኝ አገዛዝ ይሻል ነበር እያልሁ አይደለም። በፍጹም! ከታሪክ አልተማርንም፤ የዐመፅና የግፍ ዑደቱ ቀጥሏል ለማለት ያኽል ብቻ ነው።
እኛም ብዙ አልተሻልንም። በታሪካችን ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር የለንም - በደም የተለወሰ እንጂ። “በአሮጌ አቍማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ማንም አይጨምርም” የሚለውን ቃል እንለዋለን እንጂ፣ ቀደም ሲል የነበረውን የክፋት መንገድ አሁን በድጋሚ፣ ምናልባት እጅግ በባሰ ደረጃ እየሄድንበት እንገኛለን። ለዚህም ሦስት ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል። አንደኛው፣ የታሪክና የቂም እስረኝነት ለወለደው በቀል ሥልጣናችንን መጠቀማችን ነው። ኹለተኛ ደግሞ፣ አፍቃሬ - ሥልጣንና ጥቅም የወለደው አንባገነንነት ነው። ሦስተኛው፣ በተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል ያለው የሥልጣን ሹክቻ የሚያሰነሣው ዐመፅ ነው። ያለን ልምድ በዐመፅ መተካካት ስለሆነ፣ አንዱ ለሌላውን የሚመለከተው ለህልውናው ሥጋትና ፍርሃት በሆነ መልኩ ነው።
እንደምናስተውለው፣ የዐመፅ የፓለቲካችን ሽግግሮች ሁል ጊዜ አፍርሶ ከወለል የሚጀመሩ ናቸው። በመልካሙ ላይ የምንገነባ፣ ደካማውን የምናሻሽል፣ ከመጥፎው ደግሞ የምንማር አይደለንም። ይልቁንም ላለፈው ትውልድ ኀጢአት፣ ተከታዩን ተጠያቂ እናደርጋለን። መልካም ዝክር ቢኖር እንኳን፣ በሕዝብ ልብ እንዳይኖር መታሰቢያውን እንጠፋለን። በዚህ ሳቢይ እንኳን ለአገር፣ ለዓለምም ሊተርፉ የሚችሉ በርካታ መሪዎችንና ምሑራንን አጥተናል።
አስከፊ ድኽነት ይሳለቅብናል፤ በየባዕድ ምድሩም በስደተኝነት ያንከራትተናል። የሰላም እጦትና የፍትሕ ጩኸት በየምዕራቡ ዓለም አገር መንግሥታት መቀመጫ ደጃፎች ያስጮኸናል። በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ ረገጣ፣ በተደራጀ አገር ዘረፋ እና በአገር ውስጥ ስደተኝነት ደረጃ አስከፊ ከሚባሉት አገሮች ተረታ ከፊተኞች ነን። የብዙ ሺህ ዓመታት አኩሪ የነጻነት ታሪክ አለን። ኾኖም ሰው በዘር (በዘውግ) ማንነቱ ብቻ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቈጥሮ የሚፈናቀልባትና የሚጨፈጨፍባት የብዙ ምፀት ምድር የሆነች አገር ነው ያለችን።
ከትግራይ፣ ከአፋርና ከአማራ የጦር ሜዳ ውሎዎች ማግሥት፣ በአማራ ክልል የተነሣው የጦርነት እሳት፣ እኛም ከፍ ሲል በኤርምያስ ላይ እንደ ተጠቀሰው “ተንኰልን [ያለመተማመንን፣ ቂምን፣ ጥርጥርን፣ ዐመፅን] የሙጥኝ” ብለን መያዛችንን፤ እንዲሁም የሚያስከተለው ጥፋት እያወቅን ያለመመለሳችን ደግሞ የልባችንን ጥንካሬ ያሳያል።
የማሰብና የመናገር ነጻነት ፋይዳው ብዙ አልተረዳንም፤ ይልቁንም ሌሎችን በቃላት የምንገድልበት መርዝ ኾኖብናል። ይህም ምፀት ነው። ቅዱስ ቃሉ እንደሚል፤ “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።” ( ምሳሌ 12፥18 )። ክብረ-ነክ ንግግር፣ አንቋሻሽነት፣ ንቀትና ሰባሪ ትችት የቂምና የትርክት አዙሪቱን ይበልጥ አክርረውታል እነዚህ ምግባሮች እንደጥልፍ ከብዙ ብሔሮች፣ ቋንቋዎችና ሃይማኖቶች የተጠለፈውን አገራዊ አንድነት ከሥሩ አናግተውታል።
ለውጥና ሰላም ፈልገን፣ አሮጌም አቁማድ ይዘን አይሆንም። ታዲያ ከዚህ ወዴት እንሂድ?
1️⃣ ከመንፈሳዊው ልጀምር። በተደጋጋሚ እንዳልሁት፣ በቤተ እምነቶች፣ በመንግሥት እና ፓርቲዎች መካከል ግልጽ የሆነ የግዛት ድንበር ማበጀት ዋናና አስፈላጊ ነው። በተለይም ለአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ይህን ከትልቅ ትሕትና ጋር በአጽንዖት ለማሳሰብ እወዳለሁ። ለእውነትና ለፍትሕ በመቆም፣ ኀይላትን መገሠጽና መምከር የሚችሉት፣ ከፓለቲካ ተጽእኖ ውጭ በሆኑ መጠን ብቻ ነው። የፍርድ ሚዛን ሲዛነፍ፣ የአስተዳደር በደል ሲደርስ፣ ነጻ የሆነ የሕዝብ ፖለቲካዊ ምርጫ ብያኔ ሲካድ፣ ሕዝብ ለሰላምና ፍትሕ ጩኸቱ ድፍን ጆሮ ሲገጥመው፣ ቤተ ክርስቲያን ለመናገር ዐቅም የሚኖራት በራሷ ግዛት እስከ ኖረች ድረሰ ብቻ ነው። ጤናማ ያልሆነ ቍርኝትና የውለታ እስረኝነት፣ መጠኑ ቢለያይም፣ ልክ እንደ ሌሎች ቤተ እምነቶች፣ እኛንም ጐድቶናል፤ የሞራል ልዕልናም ነሥቶናል። ቆም ብለን በሰከነ ልብ ያለንበትን ዐሳሳቢ ሁኔታ ልብ ልንል ይገባል። ከየትኛውም ጊዜ በላይ ምስባኮቻችንን ከፓለቲካዊ ተጽዕኖዎች የመጠበቅ ዐደራ ወድቆብናል። ይህ እርሾ ከአሁኑ ካልተደፋ ትልቅ አደጋ አለው።
6. የአገሪቱ ፖለቲካዊ መልክ። ከደርግ ስደት ዘመናት ቀጥሎ የመጣው አንጻራዊ ነጻነት ለወንጌል ስርጭት ሰፊ በር ቢከፍትም ፖለቲካዊው ከባቢ ሙሰኛ መሪዎችን ፈጥሯል። ገንዘብ የማይጠግቡበት የሥልጣን መባለግ ወደ ሕዝቡም ተጋባ። ሕዝብ በብዙ ረገድ መሪዎቻቸውን ይመስላሉ። ሥልጣንና ገንዘብ የማይጠግቡ ሰዎች በአገሪቱ በሃይማኖት ስምም ተሰማሩ። ሕዝቡም እንዲህ ያለውን አካሄድ ተቀበለው።
7. የኑሮ ጫናና ኢኮኖሚያዊ አጣብቂኝ። በአቋራጭና በፍጥነት ባለጸጋ የሚሆኑ ሰዎች በዙ። ሚሊየነሮች እንደ ጨረቃ ቤት ተሠርተው ማደር ጀመሩ። የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ማኅበረ ሰቡን ከባህሉ አላቀቀው፤ ጨካኝ አደረገው። ሐሰተኞቹ ገንዘብ ሲያባዙ፥ በአካውንታቸው ገንዘብ እንደሚገባ ሲነገር፥ መኪና፥ ፋብሪካ ሲያዩላቸው፥ ጠንቋዮቹጋ፥ ‘በሳቸው መጀን’ እንደሚባለው ያለ ተቀባይነት ሰጣቸው። ሕዝቡ ለልማታዊ አበልጻጊ መሳይ በልጻጊ ነቢያት ካዳሚ ሆነ። መስማት የሚፈልገውን ብቻ ይሰማል፤ የጆሮ እከክ ያዘው። ሐሳውያኑም ያንኑ ይጮሁለታል፤ ይጮሁበታል። ሕዝቡ ተላጨ።
8. ሕዝባዊና ማኅበራዊ ሚድያ። ሐሰተኞች እንደ ኮርፖሬት የንግድ ኩባንያዎች በማስታወቂያ ያምናሉ። ማኅበራዊ ሚድያ ወደ አላዋቂውና አላንባቢው ሕዝብ የሚደርሱበት ዋናው መንገድ መሆኑን ደርሰውበታል። ስለዚህ ተሟሙተው አየር ላይ ሰፍረው ደመና እየጋለቡ መቆየት ትልቅ ታክቲካቸው ነው።
ስጠቀልለው፥ እነዚህ ከበርካታ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው። ከቤተ ክርስቲያን ያልተከፈለ ዕዳና ከሐሰተኞቹ መሰሪ አካሄድ በተጨማሪ ጎጋው ሕዝብ እና የሚገኝበት ከባቢ ለሐሰተኞች መፋፋት ሚናው ትልቅ ነው። ማዕከላዊው ደቡብ ደግሞ ከሌሎቹ አካባቢዎች ይልቅ የተመቸ ለስላሳ አፈር በመሆኑ ሐሳውያኑ በዚህ አካባቢ በቀላሉ መብቀል ብቻ ሳይሆን ተባዝተው መራባትም ችለዋል።
ዘላለም ነኝ።
ፎቶዎቹን ያሰባሰባቸው ማርቆስ ባሳ ነው። ማርክ አመሰግናለሁ።
ሐሰተኛ ነቢያት ስለምን በመካከለኛው ደቡብ ኢትዮጵያ በዙ? ክፍል ሁለት
በክፍል አንድ ለሐሰተኞች በመካከለኛው ደቡብ የደቀ መዝሙርነት አለመኖር ምክንያት መሆኑን አውስቻለሁ። ክርስትና ከመጀመሪያው ትውልድ ዋጋው ተቀንሶ ለቀጣይ ትውልድ እና ትውልዶች ሲተላለፍ እየመነመነ በብዙ ወረርሽኝ ይወረራል። ችግሩ ደቀ መዝሙር አለመሆንና አለማድረግ ከሆነ መፍትሔው ደግሞ ደቀ መዛሙርት በማድረግ ታላቁን ተልእኮ መወጣት ነው። ይህ ትልቅ ትኵረት ሊሰጠው የተገባ ጉዳይ ነው። የታላቁ ተልእኮ እንብርት ለራስ ደቀ መዝሙር መሆንና ደቀ መዝሙር አድራጊ መሆን ነው። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። ማቴ. 28፥19-20። ከዚህ የጎደለች ቤተ ክርስቲያን አማኞችን ለሐሰተኞች ጭዳ እንዲሆኑ እያደለበች ናት።
የዚህ የክፍል ሁለት ዋና ነጥብ ራሳቸው ሐሰተኞቹ ናቸው። እርግጥ ነው፤ ራሳቸው ደቀ መዛሙርት ተደርገው ኖሮ ቢሆን ይህን የሆኑትን አይሆኑም ነበር። እነዚህ ሰዎች የሳቱት ከተለያዩ መንደርደሪያዎች በመንደርደር ወይም በማኮብኮብ ሊሆን ይችላል። መንደርደሪያዎቹን ሦስት ቦታ እከፍላቸዋለሁ።
አንደኛ፥ አንዳንዶቹ በሰይጣን ኃይል የሚሠሩ የሰይጣን መሣሪያ የሆኑ ናቸው። ሰይጣን ብዙዎችን ለማሳት ምቹ የሚመስለውን መንገድ ሁሉ ይጠቀማል። የውሸት ምልክቶችና ትንቢቶች ደግሞ በእጁ በመዳፉ የተቀረጹ መሣሪያዎቹ ናቸው። እርሱ ከቀድሞም ሐሰተኛና የሐሰት አባት ነው። አሳች ነው።
ሁለተኛ፥ አንዳንዶቹ ሐሰተኞች ነቢያትና ሐዋርያት በእውነቱ የዋሆችና በየዋህነት የጠፉ ናቸው። የዋህ ስሕተት ግን ያው ስሕተት ነው። በስሕተት የባረቀ ጥይት ሰው ቢገድል፥ በዋህነት የባረቀ መሆኑ ሟቹን ከመሞት አያተርፈውም።
ሦስተኛ፥ አንዳንዶቹ ምንም ሌላ ምክንያት የላቸውም፤ ተንብዮ አደሮች ናቸው። ጩልሌዎች ናቸው። ግባቸውም ገንዘብና ገንዘብ ብቻ ነው። ገንዘቧን ካገኙና ካካበቱ በኋላ ከትንቢታቸውና ከድራማቸው መድረክ ይወርዳሉ። አንዳንዶቹ ቀድሞውኑ ወርደዋል፤ አንዳንዶቹም እየወረዱ ናቸው።
እነዚህ ሰዎች በአንድ የታሪክ ወቅትና አጋጣሚ ከተመቻቸ የችግኝ መፈልፈያ ከሆነው ከመካከለኛው ደቡብ ወጡ እንጂ የትም ቢሆኑ ያው ናቸው። እዚህ በብዛት ተገኙ እንጂ ከየትም ሊመጡ፥ ከየትም ሊገኙ እንደሚችሉ በመጀመሪያዎቹ ልጣፎች ከጻፉት አስተያየተኞች ጋር እስማማለሁ። በገንዘብና በጥቅም፥ በዝናና በስም ጥማት የተመረዙና የሰከሩ ሰዎች ይህንን ጥማታቸውን ለማርካት የትኛውም ርቀት አያግዳቸውም። ስለዚህ፥ ሁለተኛው ችግር ራሳቸው አሳቾቹ ናቸው። ሐሰተኞቹ የሚስቱባቸውና የሚያስቱባቸው ምክንያቶቹ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስቱ የትኞቹም ይሁኑ፥ ሁሉም የሰይጣን መጫወቻ ሜዳዎች ናቸው፤ ጎል የሚያገባባቸው ጎሎቹ ናቸው።
ነቢያትና ሐዋርያት ነን የሚሉ ሐሰተኞች 100% እስከሚባል ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያልተማሩ ሰዎች ናቸው። ስለዚህም፥ በአንዳንዶች ዘንድ፥ ‘ስላልተማሩ ነው የሚያጠፉት’ እየተባለ ይታዘንላቸውና ስለ ስሕተቶቻቸውም ይቅርታ ይጠየቅላቸዋል። ‘በኢትዮጵያ እኮ ለአቅመ አሳችነት የደረሰ ሐሰተኛ ነቢይ የለም እኮ!’ ይባልላቸዋል። ለዶ/ር ምሕረት ደበበ ምስጋና ይግባውና።
እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የላቸውም እንጂ የአሳችነት እውቀት ግን አላቸው። የሰላቢነት እውቀት ግን አላቸው። ከሰዎች ኪስና መቀነት፥ ቦርሳና አካውንት ገንዘብ እንዴት እንደሚያልቡ እውቀት ግን አላቸው። እየዋሹና ድራማ እየሠሩ ገንዘብ መሰብሰብና ጥቃቅን ነገርን በጨረታ መሸጥ ይችሉበታል። ስለዚህ፥ እነዚህ ሐሰተኞች ከመሐልም ሆኑ ከዳር፥ ከሰሜንም ሆኑ ከምዕራብ የአሳችነትን መስፈርት እስካሟሉ ድረስ የአሳችነት እውቅና ልንሰጣቸው ይገባል። ሐሰተኛ ነቢያቱ ሐሰተኛ የሆኑት ከዚህ ወይም ከዚያ ጎሳ ስለሆኑ አይደለም። እነዚህ ሰዎች የትም ብንወስዳቸው ያው ናቸው። ከየትኛውም ጎሳ ቢወለዱም ያው ናቸው። ቢመነኩሱም ዓመላቸው ያው ነው።
ይህን ክፍል ሳጠቃልል ያለፈውንም በመጥቀስ ነው። በሁለቱም ክፍሎች በመካከለኛው ደቡብ ሐሰተኞች ነቢያትና ሐዋርያት ለምን በዙ ለሚለው ጥያቄ ሁለት ምክንያቶችን አየን።
1ኛው ባለፈው በክፍል አንድ ያየነው፥ የደቀ መዝሙርነት መጥፋት ነው። የእውነተኛ ክርስትና፥ ራስን መካድ፥ ጌታን መውደድ፥ መስቀል ተሸክሞ ዕለት ዕለት የመከተል ሕይወት መጥፋት ነው።
2ኛውና በዚህ ክፍል ያየነው ደግሞ ሐዋርያት እና ነቢያት ነን የሚሉት ሐሰተኞች አጭበርባሪና አታላይ ተፈጥሯቸው አሳቾች እንዲሆኑ ማድረጉ ነው።
ሦስተኛውንና የመጨረሻውን በቀጣይ ክፍል እናያለን።
ዘላለም ነኝ።
[ጭንቀቴን ለማን ላዋየው?
አንተም እንደ ሰው ችላ ካልኸው]
.
የትላንት መንገዶች የሉኝም፣ የነገ ተስፋዎች አላበጀኹም —ምንም። ያለኸኝ አንተ ብቻ ነኽ —አንተ ብቻ። አንተ ከማየት የማታንቀላፋ ዓይን፣ ከመስማትም የማትሰለች ጆሮ ነኽ። አንተ ከመደገፍ የማትደክም ክንድ፣ ከመናገርም የማትበድል አንደበት ነኽ። ታዲያ እኔን ለምን ዝም ትለኛለኽ? ማን ያዋራት ብለኽ ፊትኽን ትመልሳለኽ? ለሰው ታካችነት ለምን አሳልፈኽ ትሰጠኛለኽ? እናት እንኳ የወለደችውን ልጅ በምትረሳበት ዓለም፣ ፍቅር እንደጠዋት ጤዛ ሳይውል በሚተንንበት ምድር ውስጥ እስከመቼ ታልፈኛለኽ? የዳዊት ልጅ እባክኽ አትለፈኝ፣ ለእኔም እዘንልኝ — አንገትኽን አዘንብልልኝ።
.
[ፍጥረት አሸልቦት
እንቅልፍም ተጭኖት
እኔ ግን ዓይኖቼ ገና አልተከደኑም
የምኀረቱን ደጃፍ እሻለኹ አኹንም]
.
የልጅነቴ አምላክ የለኽም ወይስ ግድ የለኽም? በእጅኽ አልተሠራኹም? የድንገቴ ፈጠራ ውጤት ነኝ? እንደ ዓይን ብሌንህ አትሳሳልኝም? ፍጻሜዬ ምንም ነው? ከእንስሳት ብልጫ የለኝም? በኀዘን ወደ መቃብሬ ልውረድ? ስጠፋ አይገድኽም? የማይነጠቅን ሰላም እንዳጣኹ እንዲኹ ነፍሴ ትውጣ? ታዲያ ለምን ዝም ትለኛለኽ?
ኃጢአቴ አቃተችኽ? ስለ በደሌስ ብዛት እጅኽ ከማዳን አጠረች? የእውነት ትርጉም አንተ አይደለኽም? በሕይወት የመቆየትስ ምክንያት፣ የእስትንፋሴስ ባለቤት አንተ አይደለኽምን? ግራ የተጋባችን ነፍስ ለምን በዝምታኽ ወደ ጥልቅ ትገፋታለኽ? በአጥንቴ ውስጥ አንተን መፈለግ የለም? ይኽን ግራ የተጋባ ትውልድ ሊያድን የሚወድድ የሚችልስ ማን አለ? በለሊት ወደ አንተ ስለሚቃትቱ ጎበዛዝት፣ በጠፍር አልጋቸው ላይ ስምኽን ስለሚጠሩ አዛውንት፣ ዛሬም ፍርድን ስለማያጣምሙ ንጹሐን ስትል አትመልስምን? ማን ያዋራት ብለኽ ዝም ትለኛለኽ?
.
[መቼ ነው የምንተያየው
ዓይንኽን በዓይኔ የማየው?
ቶሎ ና ዓለቴ
ባሰብኝ ናፍቆቴ]
.
መንገዱ በትርጉም ማጣት ተመትቷል። ሕፃናት ጦርነትን አውቀው፣ ቂምንም ተምረው ያድጋሉ። ድኾች ይበደላሉ። ጉልበተኞች እንዳሻቸው ይኾናሉ። ማልቀስ ብቻ አቅም ሲኾን ሕይወት እጅግ ይታክታል። ዝም ስላልኽ ረስተንሃል። ትተንሃልና ተውኸን? እንደ ሰው ? አናሳዝንህም። አለኹ አትለኝም? በቃኹኽ? ታከትኹኽ? የት ነኽ? የት ታሰማራለኽ? በሌሊትስ የት ትመስጋለኽ? ከዚኽ በላይ በድንግዝግዝ መኖር አልችልምና የት ብዬ ልምጣ? አንተ የሴተኛ አዳሪ ወዳጅ አይደለኽምን? የወንበዴውስ አፍቃሪ አይደለኽምን? እና ለምን ዝም ትለኛለኽ? ማን ያዋራኝ? ማን ያጽናናኝ? ማን መንገድ ያሳየኝ? ማንስ ከሞት ጎዳና ይመልሰኝ?
.
[ጌታ ሆይ
ጨርቅኽን ይዤ እማጸናለኹ
ከአንተ ወዴት ከቶ እሄደለኹ
ደጃፍኽ ብኖር ተጥዬ
ክብሬ ነኽ ለኔ ደስታዬ]
—————-
N.B :— ግጥሞቹ የተወሰዱት ከዶ/ር ደረጀ ከበደ የመዝሙር ስንኞች ነው።
ሄኖክ በቀለ
ነገ በኡራኤል መካነ ኢየሱስ ማኅበረ ምእመን ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ በጸሎት በጌታ ፊት አብረን እንሆናለንና የምትችሉ እንድትገኙ እንጋብዛለን።
Читать полностью…መዝሙር 46 በአንድ ትንፋሽ የሚዘመር አይደለም። ሦስት ጊዜ (ቁጥር 3፣ 7፣ 11) ቆም ተብሎ በዝምታ በማሰብና በጥልቅ አስተውሎት የተዘመረ ነው። ሴላ - Selah (ቆም ብሎ በማስብ)። ዳዊት በጊዜና በሁኔታዎች ሁሉ ላይ ሉዓላዊ የሆነውን እግዚአብሔርን ያስባል። በሕይወት ነውጦች መካከል የማይናወጠውን እግዚአብሔርን ዐለቱ አድርጓል። በርግጥ እግዚአብሔር የማይናወጥ፣ አስተማማኝና ማረፊያ በተፈለገ ጊዜ ሁሉ የሚገኝ የቅርብ ረዳት ነው! እርሱ በክፉ ቀን የማምለጫ ዐለት ነው።
ስፐርጀን መዝሙርን 46 “የዳዊት ዕንቁ” በማለት ይገልጸዋል። እግዚአብሔር ካስጨነቀን ነውጥ በላይ ‘የአሁንና የቅርብ ረዳት ነው። እግዚአብሔር ጽኑ መጠጊያነት ለዘላለም ነው። ስፐርጀን እንደገለጸው "እርሱ ብቻውን ሁሉ በሁሉ ነውና!” እውነት ነው። የሕይወታችንን መንገድና የዓለምን የታሪክ ፍሰት በልጓም የያዘ ጌታ ነው የምናመልከው።
በሚናወጠው ዓለም ውስጥ መኖራችን የማይካድ እውነት የሆነውን ያህል፣ በዚህ ነውጥ ውስጥ የእግዚአብሔር አብሮነት ደግሞ የማይካድ የእውነቶች ሁሉ አውራ እውነት ነው! የዚህም እውነት ርግጠኝነት፣ በሰላምና የደስታ ወንዝ ተምሳሌነት ተገልጧል። “የእግዚአብሔርን ከተማ፣ የልዑልን የተቀደሰ ማደሪያ ደስ የሚያሰኝ የወንዝ ፈሳሾች አሉ”። (ቁ. 4)። በሕዝቦች ዐመፅ፣ በመንግሥታት መፍረክረክና መውደቅ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ነውጥ በመካከል እግዚአብሔር አብሮነቱን ያረጋግጣል! ኢየሩሳሌም ቢታወቃትም፤ ባይታወቃትም! "እግዚአብሔር በመካከሏ ነው፤ አትናወጥም፤ አምላክ በማለዳ ይረዳታል። (ቁ. 5)
ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ እንኳ፦ ማለትም በምድር ላይ ያሉ ግዑዛንና እሰትንፋስ ያላቸው ሁሉ የታመኑበት መሠረት ቢናወጥ እንኳን፣ እግዚአብሔር የማይናወጥ የመቆሚያ ጽኑ ዐለት ነው። "ተራሮችም ወደ ባሕር ጥልቅ ቢሰምጡ፤ ውሆች ቢያስገመግሙ፣ ዐረፋ ቢደፍቁም፣ ተራሮችም ከውሆቹ ሙላት የተነሣ ቢንቀጠቀጡም አንደናገጥም።" እግዚአብሔር “ይሁን አለ . . . ሆነም” በሚለው የፍጥረት መገኛ ምክንያትን ከሆነው የእግዚአብሔር ልዕልና ኀይላነት ጋር ሲነጻጻር፣ ምድርና ነውጦቻ ነቁጥ ናቸው። አጽናፈ ዓለሙ ሁሉ - የሚታየውንም የማይታየውንም- በሥልጣኑ ቃል በፈጠረበትና ደግፎ በያዘበት በዚያው ሉዓላዊ ማዕቀፉ፣ ምድርና በእርሷም ውስጥ ያለው ሁሉ ተይዟል።
በዚህ “ሁሉ” ውስጥ - ግዙፋንና ረቂቃን፣ ያለፈው፣ የአሁኑና የሚመጣው ታሪክ ሁሉ ተካተዋል! በዚህ ምድር ላይ፣ ራሳቸው እንደ የማናወጥ ተራራ አድረገው የሚስቡ ኀይላት (ሕዝቦች፣ ፓለቲካም እኮኖሚም) ሲናወጡ፣ ጉልበታቸው ሲርድና ሲብረከረኩ፣ እግዚአብሔር ግን አይናወጠም። እርሱንም መጠጊያ ማድረግ፣ ከውስጥ ማረፈ ነው። ምክንያቱም በነውጡ ዓለም የጻድቅ እምነት ያረፈው በማይናጠው ልዑል እግዚአብሔር ነውና። እርሱ “ውሆችን በዕፍኙ የሰፈረ፣ ሰማያትን በስንዝሩ የለካ፣ የምድርን ዐፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣ ተራሮችን በሚዛን፣ ኰረብቶችንም በመድሎት የመዘነ” ነውና (ኢሳ 40:12)። ይኸው ጌታ በማዕበል በሚናወጠው የሕይወት ታንኳችን ውስጥ ከእኛ ጋር አለ - "እርሱም ተነሥቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ ‘ጸጥ፣ ረጭ በል!’ አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ ረጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ።" (ማርቆስ 4:39)። አሜን! በአጭሩ ዳዊት፣ በሸምበቆ ጥንካሬ አትደገፉ ነው የሚለን!
ሴላ - Selah - ዳዊት ቆም ብሎ ያስባል። “ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደሆንሁ ዕወቁ” - አሁን ተናጋሪው እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ነው! "ዕረፉ" የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ራፋኽ ( רפה - râphâh) የሚያሳያን፣ ራስን ለሙሉ ለእግዚአብሔር ሁሉን ገዢነት አሳልፎ መስጠት፣ በእርሱ ላይ መውደቅ። እርሱ (1) ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል። ማለትም በሁሉ አቅጣጫ የተነሣን ጦርነት ማስወገድ የሚችል እርሱ ብቻ ነው። (2) ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል። ይኽም ማለት የጉዳትና የጥፋት መሣሪያዎችን ዐቅም ያመክናል ማለት ነው! (3) ይኽ አምላክ - ያህዌ - ጅማሬም ፍጻሜም የሌለው፣ ያለና የነበረ፣ ሁልጊዜም “የአሁን አምላክ” ነው! ሌሎች አማልክት ምንጫቸው ከሚናወጠው ዓለም ሰለሆነ ከንቱ ናቸው! (4) የሰራዊት አምላክ፤ የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት ሁሉ መገኛና ገዢ፣ የያዕቆብ አምላክ፣ የእኛም አምላክ ነው።
“የያዕቆብ አምላክነት"፣ ወሰን የሌለውን የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና የተትረፈረፈ ጸጋ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን “የቅርብ ረዳትነትና የማይለወጥው የኪዳን ፍቅሩ ያሳየናል። ሴላ! ነውጦቻችንን ሁሉ በእግዚአብሔር ዕያታ ቆም ብሎ በማየት ማረፍ ይሁንልን። ~ አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
ርዕስ:- መስቀል ላይ ነው።
————————
የክርስቶስ ቤዝዎታዊ ሥራ የተፈጸመው መስቀል ላይ ነው። ክርስቶስ ጌታችን የሰውን ዘር የዘመናትን ቀንበር የሰበረው፣ የዕዳን ጽሕፈት የደመሰሰው፣ ከሳሹን ዲያቢሎስ ያዋረደው፣ ሰይጣን የሽንፈትን ካባ ለብሶ የተሰናበተው፣ ለሕዝቡ ነጻነትን ያወጀው መስቀል ላይ ነው። በኢየሩሳሌም መቅደስ ውስጥ አልነበረም። ከምኩራቦች በአንዱ ውስጥም አልነበረም። ከእጁ የበሉት “ከርሱ ጋር አልነበርንም… ከቶም አናውቀውም” ብለው ርቀው በቆሙበት በዚያ ሥፍራ የከበቡት በሸሹበት፣ የቀረቡት በራቁበት፣ የተከተሉት በከዱበት ሥፍራ መስቀል ላይ ነው። ጭብጨባም አድናቆትም ሙገሳም ውዳሴም ባልነበረበት ሰማይ ምድሩ በጨለመበት የብቸኝነት ሥፍራ መስቀል ላይ ነው።
ጌታችንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ዕውሮችን ሲያበራ፣ የተራቡትን ሲመግብ፣ ለምጻሞችን ሲያነጻ፣ ጎባጣዪቱን ሲያቀና በነበረበት ሥፍራ እንዳይመስለን። ወቅታዊ ጥያቄዎችን በመለሰበት፣ ተከታዮቹ ስሜታቸው በተነካበት፣ ተገልጋዮች ሁሉ በደስታ በፈነጠዙበት ሥፍራ ላይ አልነበረም። ጌታችን በጥብሪያዶስና በገሊላ አካባቢዎች ሲመላለስ ወይም በቅፍርናሆምና በናዝሬት መንደሮች ሲዘዋወር እንዳይመስለን። ዳሩ ግን እርቃኑን በሰማይና በምድር መካከል በተንጠለጠለበት የእሾህ አክሊል በተጎነጎነለት፣ መራራ ጽዋ በጎነጨበት፣ በፈጠራቸው ሰዎች እጅ በምስማር በተወጋበት በዚያ ጎልጎታ በተባለው ሥፍራ በዚያ ኮረብታ በቀራኒዮ መስቀል ላይ ነው።
በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት የደጋሾችን ገመና በሸፈነበት፣ ውሃቸውን ወይንጠጅ ባደረገበት፣ ተከታዮቹን ባስደመመበት፣ ታዳሚዎችን ባስጨበጨበበት፣አሳዳሪውን ባስገረመበት ሥፍራ አልነበረም ክርስቶስ ለዓለም “ተፈጸመ”ን ያበሰረው። ሺዎችን በመገበበት ከርሳቸውን አጥግቦ ተዓምር ሠራ በተባለበት፣ ርህራኼውን በገለጠበት ሥፍራም አልነበረም። በደብረ ዘይት ተራራ መልኩ በተለወጠበት ክብሩ በታየበት ጴጥሮስ “እዚህ መሆን ምርጫችን ነው” ባለበት በዚያ ሥፍራም አልነበረም። ወደ ምድር የመጣበት ዓላማው ግቡን የመታው ከነዚያ ሥፍራዎች በየትኛውም ሳይሆን ክርስቶስ ጌታችን “ተፈጸመ” ያለው መስቀል ላይ ነው። መስቀል ላይ ነው።
መስቀል አልባውን የቃና ዘገሊላ ክርስትና፣ መስቀል አልባውን የዓሳና የዳቦ ክርስትና፣ መስቀል አልባውን የምቾትና የስኬት ክርስትና መስቀል አልባውን የጭፈራና የዘንባባ ክርስትና ሰይጣን አያሳድደውም። መቼም አይቃወመውም። ከቶም አይጠላውም። ለምን ብሎ? አጃቢው ብዙ ነው። አጨብጫቢው አሸን ነው። ክርስቶስን ከምንም በላይ በዚህኛው ውለታው የምታውቁ ተሰዳጆች ሆይ ደስ ይበላችሁ። የእኛ እምነት መሠረቱ ይኼ ነው የኛ ስብከት መሠረቱ ይኼ ነው። “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።” (ቆላ. 2:14) ቆላስይስን አንብቦ ሲያበቃ ስለ ግንብ ቤት፣ ስለ መርሰዲስ መኪና ስለ ባንክ ቡክ የሚናገር ሰባኪ ክርስትናው የክርስቶስ ይደለም።
በመሆኑም ፊታችሁን አይተን የማንቀይረው መልዕክታችን፣ ለስሜታችሁ መኮርኮር ብለን የማናቀርበው ትምህርታችን የተሰቀለው ክርስቶስ ነው። የቀደሙን የርሱ አገልጋዮች “ምሰሉን” ያሉን ሐዋርያቱ ከክርስቶስ በቀር ሌላ ላለማወቅ የቆረጡቱ ወንድሞቻችን ስብከታቸው ትምህርታቸው ትምክህታቸውም የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻ ነበር። “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” (ገላ. 6:14) ብለዋል። እኛም ያንን መስመር አጥብቀን ይዘናል። ቁም ነገሩ ያለው መስቀል ላይ ነው። በተሰቀለው ነው። The cross, then the crown!
መልካም ቀን!!
ወርቅነህ ኮየራ
"በህብረቱ" ተስፋ ቆርጫለሁ!
ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚንስትሩ "ከወንጌላዊያኑ" መንደር (ሃሳዊ ኢሃሳዊ ሳይሉ) በድንገቴ የጅምላ ጥሪ በርከት ያሉ "አገልጋዮችን" ይዘው በቤተመንግስታቸው ስብሰባ እንደተቀመጡ እናስታውሳለን። በስብሰባውም ቀን "ሰብሰብ በሉ.. አንድ ላይ ሁኑ..." ወዘተ የሚሉ ምክረ ሃሳቦችን "ለወንጌላዊያኑ" እንዳቀረቡ እና "ሰብሰብ ማለቱንም" የሚያሳልጥ "አመቻች ኮሚቴ" ራሳቸው እገሌ እገሌ ብለው እንደመረጡም ጨምረን እናስታውሳለን።
"አመቻች" የተባለውም ኮሚቴ የማመቻቸትና "የማመቻመች" ስራውን በአጭር ጊዜ አጠናቆ "የወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስል" የሚል በግና ተኩላውን በአንድ ጎረኖ የሚያሳድር ተቋም መመስረቱም የሚዘነጋ አይደለም። በዚህም ሂደት ቀደም ሲል "ለወንጌላዊያን" እንደ ወኪል ይቆጠር የነበረውም "የወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ህብረት" በካውንስሉ ስር መታቀፉ ተበሰረ።
ነገር ግን ከጥቂት ጊዜያት በኋላ "ህብረቱ" በወንበር ድልደላው "አልተስማማሁም" በሚል ሰበብ ከካውንስሉ ጥሎ መውጣቱን ይፋ አደረገ። አያይዞም "ካውንስሉን" የሃሳዊያን ተባባሪ፣ ወንጌልን ለሚሸቅጡ ዋሻ መሆኑን እየጠቀሰ በየሚዲያው ይወቅሰው ያዘ። አንዳንዶቻችንም ይህንን "የህብረቱን" አቋም ደግፈን ፃፍን፣ ተናገርን፣ ተከራከርን። "በህብረቱ" እና "በካውንስሉም" መካከል የነበረው አለመግባባት በበርካታ የአደባባይ ንትርኮች የታጀበ ስለነበረ ግንኙነታቸው ያበቃለት አድርገን ወሰድነው። "ህብረቱም ክፍተቱን እያረመ ወንጌላዊውን ክርስትና የሚወክል ጠንካራ ተቋም ሆኖ ይወጣል" በሚልም ተስፋ ሰንቀን ሰነበትን (በበኩሌ በብዙ ተስፋ ነበርሁ)።
ነገር ግን ይህ "የህብረቱ" ሁኔታ አልዘለቀም። የካውንስሉ ወላጅ አባት እንደገና ውይይት እንዲያደርጉና ችግራቸውን እንዲፈቱም አሳሰቡ። ህብረቱም ቢሆን የቀድሞው ድብቅ ጥያቄው "የወንበር ቁጥር" ጉዳይ እንጂ "ከሃሳዊያን ጋር ምንም ዓይነት ህብረት አታድርጉ" የሚለው መለኮታዊ ትዕዛዝ ስላልሆነ "በወንበር ተደራድሮ" ወደ ካውንስሉ መጠቃለሉን በመግለጫ ነገረን። ስለዚህ ከዚህ በኋላ "ካውንስሉ" እንጂ "ህብረቱ" የለም! ማለት ነው።
አንዳንዶች "የህብረቱን" ወደ "ካውንስሉ" መግባት "ስትራተጂ" አድርገው ሊመለከቱት ሞክረዋል። "የወንበር ድልድሉም ከፍ ለማስደረግ የታገለው ውስጥ ገብቶ በድምፅ ብልጫ ሃሳዊያኑን በጊዜ ሂደት ለማስወገድ ነው" የሚል ሙግትም ያቀርባሉ። ነገር ግን ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከሃሳዊያን ጋር ምንም ዓይነት ህብረት እንዳናደርግ በግልፅ ከተሰጠው መፅሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ጋር በቀጥታ የሚጋጭ እንደሆነ ማስተዋል ጠቃሚ ነው። ደግሞም መፅሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆነ መንገድ ሄዶ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም።
ስለዚህ በእኔ ግምገማ መሠረት "ህብረቱ" በ "ካውንስሉ" ተውጧል። ተስፋ የለውም። ከዚህ በኋላም ወንጌላዊያንን የሚወክል መፅሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ላይ የቆመ ምንም ዓይነት ተቋም የለም! ብሎ መደምደም ይቻላል። "ካውንስሉ" ወንጌላዊያንን አይወክልምና!
ታዲያ ምን እናድርግ?
የሚሻለው "ብዙዎች ዋጋ ከፍለው የሰጡንን ወጌላዊውን ክርስትና ከካውንስሉ እና ከሃሳዊያኑ አቅጣጫ በተደራጀ መልክ የሚደርስበትን ጥቃት ተከላክለን ለቀጣይ ትውልድ ልናሻግረው የምንችልበትን መንገድ መፈለግ ላይ መወያየት ብቻ ነው።
በአሁኑ ጊዜ እንደ ወንጌል እውነት የቆመ እና ወንጌላዊውን ክርስትና የሚወክል ተቋም የለም!
ቴዎድሮስ ተጫን