ይህ ስምምነት ብዙ ጠቃሚ ትብብሮችን ይዟል። ሆኖም ለከፋ ችግር የሚያዘጋጀን ዕቅድ እንዳለውም ልብ ልንል ይገባል። ብዙ ጥበብና ማስተዋል የሚጠይቅ እርማት ያስፈልገዋል። የምዕራቡ ዓለም “የሰው ልማትና ዕድገት” እሳቤ እግዚአብሔር የለሽና ሰውን የራሱ አምላክ ያደረገ ዓለማዊነት (Secular Humanism) ነው። እውነተኛ “የሰው ልማት” ፈሪሓ- እግዚአብሔርን እንዲሁም የሰውን አምሳለ መለኮት ተሸካሚነት ያማከለ ነው። እናስተውል፣ በጥቂቶች በተያዘው የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ ብልጽግና አብላጫውን የዓለም ሕዝብ ጨቍኖ ያያዘና ኢፍትሐዊ ነው። በምዕራቡና በቀረው የድኾች ዓለም መካከለ ልክ እንደ የሰማይና የምድር የርቀት ከፍታ ያህል ያለው የሀብት ክፍፍል ልዩነት ይህን ሐቅ ያመለክታል።
ለቤተ ክርስቲያን - ይህን ስምምነት የሚያጠናና ነገረ መለኮታዊ እንድምታዎቹን የሚያሳየን የባለሙያዎች ስብስብ በመፍጠር ሕዝብን ማንቃት እንዲሁም መንግሥትን መመከር ያስፈልጋል። ትልቅ አደጋ በፊታችን አለና! በብዙ ሞራል ዝቅጠት ውስጥ በተዘፈቀ፣ አምላክ የለሽ፣ እውነት አንጻራዊ ሆኖ በደበዘዘበት የምዕራቡ ዓለም ባህል ተጽእኖ ሥር ለሚያድጉ ልጆቻቻንንና ለመጨው ትውልድ ልናስብ ይገባናል። በእርዳታና በሰብአዊ መብት ሽፋን በአገራችን ላይ ያኮበኮበውን የምዕራቡን ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም አጀንዳ በቸልተኝነት ብንሳልፍ መዘዙ የከፋ ነው የሚሆነው። በዘረኝነት፣ በክፍፍል፣ በሐሰት አስተምህሮና በዓለማዊነት እንቅርት ላይ፣ ልጆቻችንን ሊበላ ያኮበኮበው የሞራልና የወሲብ ልቅነት አውሬ ተጨምሮበት ምን ይተርፈናል? ቤተ ክርስቲያን ስትወደቅ ትውልድም አብሮ ይወድቃል። ወደ ወንጌል እንመለሰ፤ ለትውልዱም ብርሃንና ጨው እንሁን!
ለቤተ ሰብ - እንንቃ፤ እንጸልይ! በጋብቻ፣ በጾታ ማንነትና በቤተ ሰብ እሴቶቻችን ላይ ግልፅ ጦርነት ታውጇል። ልጆቻችንን በቃልና በሕይወት ምስክርነት እናስተምር። እኛ ካላስተማርናቸው፣ ክፉው ባህል ያስተምራቸዋል። ልጆቻችንን ቄሳር ሳይሆን፣ እኛ ነን ልናሳድግ የሚገባው። እንደምናስተውለው፣ በምዕራቡ ዓለም ነውር የሆነው በአደባባይ በሕጋዊ ፈቃድ ይከበራል፣ ክብር የሆነው "እንደ ነውር" በሕግ ተከልክሎ ይሰደዳል። ነግ በእኛ ነው፤ እናሰብ፤ በቤታችን ክርስቶስና ቃሉ ይሰልጥኑ!
ለመንግሥት - በዚህ ስምምነት አንቀጽ 99 መሠረት እርማት መጠየቅ ይቻላል። በስምምነቱ በተነሱት ስድስት ዐብይት ርእሰ ጕዳዮች ለአገራችን ያላቸው ፋይዳ በባለሙያዎች የሰከነ ጥናት የተደረገ ይመስለኛል። ሆኖም በዚህ አነስተኛ ጽሑፍ ላይ እንዳነሳሁት ጾታን፣ ወሲብን፣ ውርጃን፣ ሰብአዊ መብትንና የጾታ ጤና ትምህርትን አስመልክቶ የአገሪቱ አረዳዳ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። የስምምነቱ አንዱ ትልቁ ችግር ቃላት ዐውዳዊ አፈታት እንዳላቸው ግምት ውስጥ ያለማስገባቱ፤ ወይም ሆነ ብሎ መተው ነው። የአገራችንን አረዳድ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። ሰላም፣ ፍትሕና የአገር ብልጽግና አይለያዩም። በፍትሕ፣ በሰላም፣ በይቅር ባይነት፣ በዕርቅና በፈውስ ላይ ወደ ተመሠረተ አገራዊ መግባባት መሄድ ይገባናል። የዐመፅ ዑደት የመሰበሪያው መንገድ ይኸው ብቻ ነው። የድኽነት ቀንበራችንን ይበልጥ ካከበደው ዐመፅ-መር የፓለቲካዊ አዙሪት መውጣት አለብን። በእርዳታ የበለጸገ አገር የለም፤ በሰላም ዋስትና፣ በፍትሕ መስፈን፣ በሕግ የበላይነት መሰልጠንና በሥራ ትጋት እንጂ። በአንድ ጊዜ እርዳታ ፈላጊና የእርዳታውን ውል ተደራዳሪ ልንሆን አንችልም።
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ያድስ፤ አገራችንን ይባርክ፤ ይጠብቅም!
አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት - (ዘፍጥረት 4 ፥ 7)
በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራትና በአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገራት (OACPS) መካከል በ 403 ገጾች የተካተተ ለ 20 ዓመታት የሚዘልቅ ታሪካዊ የአጋርነት ስምምነት (OACPS-EU Partnership Agreement, 15 November 2023) በ አፒያ ሳሞዐ ተፈርሟል። ስምምነቱ ከ 20 ዓመት በፊት በኮትኑዩ፤ ቤኒን የተፈረመውን ስምምንት (The Cotonou Agreement, 23 June 2000) የሚተካና፣ በስድስት አንኳር ጕዳዮች ላይ አሳሪ መርሕ ይሆናል። እነዚህም ሰብአዊ መብቶች፣ ዲሞክራሲና አገረ መንግሥት፣ ሰላምና ደኅንነት፣ የሰውና የማኅበራዊ እድገት ልማት፣ ዘላቂ የተፈጥሮ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የሰው ፍለሰት እና እቅስቃሴን በተመለከተ ነው።
ከፍ ሲል በተጠቀሱት የስምምነት ነጥቦች ላይ ያለኝ ግንዛቤ ከአጠቃላይ ዕውቅት ያለፈ አይደለም። ስምምነቱ ለአገራችን ያለውን ፋይዳ፣ ዝርዝር ትንተናና እንድምታ ለባለሙያዎቹ እተዋለሁ። ሆኖም አስፈላጊነቱን በጽኑ አምናለሁ። ትኵረቴ ሰብ አዊ መብትንና አካታችነትን ተንተርሶ በቀረበው የጾታ ማንነትና የወሲብ እሳቤ ላይ ነው። እጅግ አሳሳቢና የማኅበረሰብን በተለይም የጾታ ማንነትን፣ የወሲብ ትምህርት፣ የጋብቻንና የቤተ ሰብን መሠረት ከሥሩ የሚያናጉ ፖሊሶዎችን ይዟል። ይህን አስመልክቶ ያስተዋልኳቸውንና ትኵረት የሚሻቸውን የስምምነቱን ነጥቦች በአምስት በመክፈል እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
1) ያልተገደበና አካታች የጾታ ማንነትን “የሚያከብር” ሰብአዊ መብት ተግባራዊ ማድረግ
ባለ ደርሻ አካላት፣ ማለትም በአንድ ጐራ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት፣ በሌላኛው ጐራ አፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገራት፣ “ለሰብአዊ መብቶች” መከበር በጋራ እንደሚሠሩ በአጽንዖት ተሰምሯል። በተለይም የተባበሩትን መንግሥታትና የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት (OECD) መርሖች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው የሚያግዙ ፖሊሲዎችና ደንቦች፣ በግል፣ በማኅበራዊና በባህል ዘርፉ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ማረጋገጥ ነው። ይህም ማለት በሥራ ላይ ያሉት የአገራት ፖሊሲዎች፣ ድንጋጌዎችና ደንቦች በዚህ አግባብነት በየጊዜው ይቃኛሉ (አንቀጽ 2፣ ቍ. 5፤ አንቀጽ 4፣ ቍ. 1፤ አንቀጽ 9፣ ቍ.2፤ አንቀጽ 13፣ ቍ. 5፤ አንቀጽ 20፤፣ ቍ. 5)።
እንደሚታወቀው ከ 38ቱ የ OECD አገራት 24ቱ የግብረሰዶም ጋብቻን ያጸደቍ.፣ እንዲሁም የድርጅቱ የውጪ እርዳታ ፓሊሲ ይህንኑ አካታች እንዲሆንና ተረጂ አገራትም “በሰብአዊ መብት” ሰበብ እንዲቀበሉት ጫና ያደርጋሉ። በአገራች ሰላም፣ ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነትትና ሰብአዊ መብቶች መከበረ የወቅቱ የአገራችን ዐቢይ ጥያቄዎች ናቸው። ሆኖም ስምምነቱ የሚጥይቀው “ያልተገደበና አካታች የጾታ ማንነት መብት” ችግራችን አይደለም። ቢያንስ የአብዛኛው ሕዝብ።
2) የምዕራቡ ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም (Gender Ideology) ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ
ስምምነነቱ እ. ጐ. አ በ 2030፣ ድኽነትን ማጥፋት፣ ጾታዊ አድሎአዊነትን ማስቀረትና የጾታ [Gender] እኩለነትን ማረጋጥ ግብ ያደርጋል። ለዚህም አፈጻጸም ይረዳ ዘንድ፣ ባለ ደርሻ አካላት በኅብረተሰባቸው መካከል ያሉ “የተዛቡ የጾታ ዕይታዎችን” ማስተካከል፣ እንዲሁም የጾታን ማንነትን፣ መብትንና እኩልነትን በተመለከተ በፓሊሲዎችና በፕሮግራሞች ሁሉ ውስጥ ማስረጽና ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋል። (አንቀጽ 2፣ ቍ. 5፤ አንቀጽ 9፣ ቍ. 2፤ አንቀጽ 10፣ ቍ. 1፤ አንቀጽ 41፤ አንቀጽ 80፣ ቍ. 3)።
ለመሆኑ የምዕራቡ ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም በአጭሩ ምንድነው?
የዚህ ርዕዮተ ዓለም “የወሲብ አብዮት አባት” በመባል የሚታወቀውና ከዚህም ጋር ተያይዞ የምዕራቡን ዓለም የጾታና የወሲብ ግንዛቤ፣ ዕሴቶችና ባህል ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የቀየረው የኢንዲያናው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አልፈርድ ሲ ኪንዚ (June 23, 1894 — August 25, 1956) ነው። በተለይም “የኪንዚ ሪፖርት” በመባል የሚታወቍት Sexual Behavior in the Human Male (1948) እንዲሁም Sexual Behavior in the Human Female (1953) “የምርምር ሥራዎች” ለምዕራቡ ዓለም ወሲባዊና የጾታ ማንነት ቀውሶች ትልቅ አስተዋጾኦ አድርገዋል።
ሁለተኛው ሰው ትውልደ ኒውዚላድ የሆነ አሜሪካዊው ጆን መኒ (8 July 1921–7 July 2006) ነው። መኒ በጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል ታዋቂ የሕፃናት ሕክምናና የሥነ ልቡና ፕሮፌሰር ነበር። በግብረ ሰዶም ወታደራዊ አራማጆች ዘንድ “የጾታ ለውጥ ንቅናቄ መንፈሳዊ አባት (the spiritual father of trans movement)” በመባል ይታወቃል። በምዕራቡ ዓለም ያለው “የጾታ ለውጥ” ሕክምና ሳይንሳዊ ፍልስፍና መሠረት ያረፈው በዚሁ በጆን መኒ ሥራዎች ላይ ነው።
“ጾታ ተፈጥሮአዊ ሳይሆን” ማኅበራዊ ውቅር (social construct)” ነው የሚለው የጾታ ርዕዮተ ዓለም (Gender Ideology] ፊት አውራሪ ነበር። መኒ “ወንድነትም ሆነ ሴትነት” ምርጫና ማኅበራዊ ውቅር እንጂ ተፈጥሮአዊ አይደለም የሚል ጽኑ እምነት ነበረው። ልጆች ጾታ “ገለልተኛ ሆነው እንደሚወለዱ” (born gender neutral)፣ ምንም ተጽዕኖ በማያመጣ መልኩ “ጾታቸውን” በሕክምናና በቴራፒ መቀየር እንደሚቻል ይሞግታል። በ1965 በአሜሪካ ያቋቋመው የመጀመሪያው የጾታ ዝውውር ቀዶ ጥገና (sex reassignment surgery) የሕክምና ፍልስፍና መሠረት ይኸው የተጣመመ ግንዛቤ ነበር። ኪንዚም ሆነ መኒ በወሲብ ጕዳይ በራሳቸው እጅግ ግራ የተጋቡ፤ ከሁለቱም ጾታዎች፣ እንዲሁም የጾታ ለወጥ ካደረጉ ጋር ክፍትና ያልተቆጠበ ግኑኙነት ነበራችው።
የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች (UN Women) የሰብአዊ መብቶች ሙግት መሠረት ያረፈው በኪንዚና በመኒ ሥራዎች ላይ ነው። ለምሳሌ፣ “ጾታ [ወንድነትና ሴትነት] ሥነ-ተፈጥሮአዊ ሳይሆን” ማኅበራዊ ውቅር (social construct) በመሆኑ በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆነ ብዙ ዐይነት መገለጫዎች አሉት” (UN Women: United Nations Entity for Gender Equality) የሚል ጽኑ እሳቤ አለው። በአሁኑ ወቅት በምዕራቡ ዓለም አተርጓጐም “ጾታዊ ማንነቶች” እስከ 107 ደርሰዋል። በዚህም አያበቃም። በዚህ ስምምነት ውስጥ የተሰወረው “ሰይጣን” የእነዚህ ሁለት ሰዎች ሥራ ነው። ቅዱስ ቃሉ እንደሚለው “ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው፤” (ዘፍ 1፥27)። ወንድ እና ሴት እኩል ናቸው፤ አንድ ዐይነት ወይም ተለዋዋጭ ግን አይደሉም። የማኅበረ ሰብ መሠረት ቤተ ሰብ ነው፤ የቤተ ሰብ መሠረት “የወንድ እና የሴት” እኩልነትና ጾታዊ ልዩነት ነው። በዚህ ስምምነት አማካኝነት “በሰብአዊ መብትን” በመንተራስ ይህን ዘላላማዊ እውነት የሚያፈርስና የቤተ ሰብን፣ የማኅበረሰብንና የአገርን መሠረት የሚናጋ ዕቅድ ወደ አገራችን እየመጣ ነው። እናስተውል፤ እንንቃ! ድኽነትን በጋራና በትጋት እየተዋጋን ፈሪሓ-እግዚአብሔር ያለው ትውልድ ማትረፍ ይሻለናል።
3) ሥርዐተ ትምህርቶች “በተሟላ የጾታ ትምህርት” እንዲቀረጹ ማድረግ - Compressive Sex Education
የ SIM የኢትዮጵያ ዲሬክተር የነበሩት ነዊ ዚላንዳዊው ብሩስ ቦንድና ባለቤታቸው ኖሪን፣ የአገልግሎት ዘመናቸው እንዳለቀ የባቦጋያን የአገልጋዮች ማረፊያ በኀላፊነት ለማስተዳደር ተሰማርተው ነበር። እጅግ ትሑት፣ ጌታንና ቤተ ክርስቲያንን የሚወዱ በዝቅታ መንፈስ ያገለገሉ ሚስዮናዊ ነበሩ።
ወደ ባቦጋያ ማሪፊያ በደስታ ነበር የሄዱት። ዋናው ተግባራቸውም በአገልግሎት የሚባክኑ መሪዎች ለእረፍት፣ ለጸሎት ወይም ለምክክር ሲመጡ ማገልገል ነበር። በኋላ እንደ መሰከሩት፣ እግዚአብሔር ትልቅ ዓላማ ነበረው። ባቦጋያን ማሰተዳድር ለላቀ ራእይ መንገዱ ነበር። በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ኩሪፍቱ ማዕከል ራእይ ፊተኛ ጀማሪ ሆኑ። ይህን ራእይ በወቅቱ ከነበሩት የደብረ ዘይት ቃለህይወት ቤተክርስቲያን መሪዎችና ከዋናው የቃለ ሕይወት ጽ/ቤተ ጋር በመመካር የበለጠ አዳብረውት እንደ ነበረ አስታውሳሁ። ከብዙ ምክክርና ጸሎት በኋላ ማዕከሉን ለመገንባት ለመንግሥት ጥያቄ ቀረበ። እንኳን የሚቻል፣ የሚሞከረም አይመስልም ነበር.። በሚገርም ሁኔታ የደርግ መንግሥት በሕጋዊ ፈቃድ ቦታውን ለቤተ ክስቲያኒቱ ሰጠ። ይህ ክንውን የእግዚአብሔርን ኀይለ ልዕልና፣ ረድኤትና ሞገስ ያሳየ ነበር።
የልማቱን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችሉ ዕቅዎችን የያዘው ኮንቴይነር ሥፍራው እንደ ደረሰ፣ በቦታው ላይ በደስታና በተስፋ በታጀበ እንባ ጸሎት ተደርጎ ነበር። ፊተኛ ሆነው የመሩ የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች ዶ/ር ሙላቱ ባፋ፣ አቶ ጥላሁን ኀይሌ፣ ጋሽ ተክሌ ወለደ ጊዮርጊስ አንዲሁም ብሩስ ቦንድ ነበሩ (ሁሉም አሁን በጌታ ዕቅፍ ያሉ) ። በእግዚአብሔር ቸርነት የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች አገልግሎትን በመወከል ያንን ታሪካዊ ጸሎቱ ለመካፈል ጌታ ዕድል ሰጥቶኝ ነበር።
ደርግ ነጣቂ እንጂ ሰጪ አልነበረም። ፈጽሞውኑ የቤተ ክርስቲያን ወዳጅ አልነበረም። ሆኖም ትእዛዝ በችሎታው ታላቅ ከሆነው ከላይ ከጌታ ዘንድ ስለመጣ ብቻ የቤተ ክርስቲያኒቱን ራእይ ለመደገፍ ቀኝ አጅን ሰጥቶ ነበር። እውነት ለመናገር ጥቂቶች ይሁኑ እንጂ፣ ቀና የነበሩ የከተማና የፌደራል ባለሥልጣናትም ነበሩ።
አገራችን የሕግ የበላይነት እጅግ የላላባት ምድር ሆናለች። ቃለ ሕይወትን ጨምሮ፣ ከቦታ ይዞታና የአምልኮ ነፃነት ጋር በተያያዘ በርካታ አብያትተ ከርስቲያናት የሚያልፉበት እንግልት እጅግ አሳሳቢ ነው።
በሌላ ዐውድም ቢሆን የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ሕግን የጣሰ ተግባር፣ የናቡቴን መሬት በግፍ የወሰዱውን የአክዓብንና የሚስቱን የኤልዛቤልን መንግሥት የጭከና መንገድ ያስታውሰኛል። ጥያቄአቸውም፣ “ቦታህ የአትክልት ቦታ እንዳደርገው ልቀቅልን” ነበር። የናቡቴ ንጹሕ ደም ፈሰሰ፣ ቦታውንም በሐሰትና በግፍ አጣ። ይሁን እንጂ ድርጊታቸው ከእግዚአብሔር የተሰወረ አልነበረም። ይልቁም ነብዩ ኤልያስ እንዳለው፣ “በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ” ነበር. (1 ነገሥት 21)።
ልባችን እጅግ አዝኗል። እንጾማለን፣ እንጸልያለን፣ ድምፃችንን እናሰማለን። የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ሆይ፣ እባካህን እግዚአብሔርን ፍራ! እርሱ "በጽድቅ ይዳኛል፤ ለተቸገሩትም በትክክል ይፈርዳል። (መዝሙር 72 : 2 )
“በኪሩቤል ላይ በዙፋንህ የተቀመጥህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህም አንተ ነህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይንህንም ክፈትና እይ” (2 ነገሥት 19: 15-16)
የክርስቶስ ሰላም በምድራችን ይንገሥ፤ ፍትሕም ይስፈን!
አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
«መዝሙር ኃጢአት ነው» | «ዘማሪዎቻችንን ማን ዝም ያሰኝልን?»
ድሮ ድሮ በወንጌላውያን አማኞች ወይም በተለምዶ በፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዘንድ ዘፈን እጅግ ጽዪፍና እርም የኾነ ኃጢአት ነበር። እየዋለ ሲያድር ግን ኤልያስ መልካና መሰሎቻቸው በተግባር እንዲኹም እነ ዮናስ ጎርፌ መጽሐፍ በመጻፍ ጭምር የደገፉት የ«ዘፈን ኃጢአት አይደለም» አብዮት ተፋፋመ። ይኽ አብዮት ዛሬ አብዛኛው ወንጌላዊ አማኝ ወጣት ስለ ዘፈን ለዘብተኛ አቋም እንዲይዝ ሰበበ ምክንያት ኾነ።
የወንጌላውያን አማኞች ተጽዕኖ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ቀላል የሚባል አይደለም። በደንብ ቢጠናና ቢታሰስ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ግማሽ በግማሽ፣ በተለያየ ቅርጽና መልክ የፕሮቴስታንት (የወንጌላውያን አማኞች) ቤተ-ክርስቲያን እዳ ያለበት ነው።
ድሮ ድሮ ቸርች አስተምራና አሠልጥና ያበቃቻቸው ሙዚቀኞች አንድም የተሻለ ክፍያ ፍለጋ፣ ኹለትም የሙያዊ ክወና መሻት ገፍቷቸው ወደ ዓለማዊው ሙዚቃ ይቀላቀሉ ነበር።
አኹን ግን እነዚኽ ኹኔታዎች ተለወጡ። አባትና እናት እንዲኹም መሠረት የሌላቸው ስሑት ቸርቾች በየቦታው መፈልፈላቸውን አያይዞና የገንዘብ አቅማቸውም እነዚኽን መርሕ አልባ፣ አቋም-አልባ፣ … ካድሬያዊ የአድር ባይነት መንፈስ የተጠናወታቸውን “ዘማሪዎች” በንዋይ ብዛት አሳክረው አሟቂ አሟሟቂ ያደርጓቸዋል። ሌላው ደግሞ ሥርዓትና ቅጥ፣ በልክ መኾንና በመንፈስ ማምለክ ስለማይታወቅ በዘፈን ውስጥ «አስረሽ ምቺው» ሊሉ የተዘጋጁባቸውን ቴክኒኮች ኹሉ እዚኹ ቸርች ተብዬ ቦታዎች ይጠቀሟቸዋል። የመጠን አልባነቱ ጉዳይ ብሶ ተባብሶ እንደ መሸታ ቤት ግንባር ላይ ብር መለጠፍ ብቻ ቀርቶናል። ስለዚኽ ዓለማዊ ሙዚቃን የሚከጅሉበት ምክንያት አይኖራቸውም። ዛሬ «አልተውኽም ጌታ» ያሉት የምቾት ዘመን ውልዶች ድሮ ቢኾን ወደየናይት ክለቡ የሚጎርፉ ተቀጥላዎች ነበሩ።
ሃይ ባይ ገላጋይ እስካልተገኘም የቀደሙ ውብ ዝማሬዎች በፈሰሱባቸው እምነተ መድረኮች ላይ ወጣት ደፋሮች እየፈነጩባቸው ይቀጥላሉ።
እኔም ጽሑፌን ጳውሎስ ፍቃዱ ከዐሥራ ምናምን ዓመት በፊት በካሪዝማ መጽሔት (?) ላይ ባቀረበው መጣጥፍ ርዕስ ዘጋለኹ
«ዘማሪዎቻችንን ማን ዝም ያሰኝልን?»
ሄኖክ በቀለ
የሚደነቅ ትክክለኛ እርምጃ! እናመሠግናለን!
በስመ ክርስትና የሚሰራጨው የብልፅግና ወንጌል መሠረታዊ አስተምህሮ በ"Word of faith" እና "Name it and Claim it" በሚሰኙ መርሆች የተቃኘ ነው። ይህ አስተምህሮ እነ ዳዊት ድሪምስና ነፃነት ዘነበ ከሚከተሉት የስበት ሕግ በዋናነት የሚለየው በምንጭ አጠቃቀስ ሲሆን ከዓላማውና ግቡ አኳያ ግን ተመሳሳይ ነው። የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች ለአስተምህሮአቸው ትክክለኛነት መፅሐፍቅዱስን አጣምመውና አዛብተው ሲተረጉሙ፣ እነ ዳዊት ድሪምስ ደግሞ ለክርስቲያኑ ማህበረሰብ የመፅሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች አለቦታው ከመጠቀም በተጨማሪ ለአስተምህሮአቸው ሳይንሳዊ ካባን ለማጎናፀፍ የኳንተም ፊዚክስን ከአውድ ውጭ አጣምመው ይተረጉማሉ።
ይህ ከሥር የምትመለከቱት የብልፅግና ወንጌል(ወንጀል?) ሰባኪ የሆነው ጎረምሳ ሰሞኑን "የፋይናንስ ጥርመሳ" በሚል ርዕስ ኮንፍራንስ ለማዘጋጀት ተፍ ተፍ ሲል ነበረ፤ ሆኖም ኮንፍራንሱን የሚያካሄድበት አካባቢ(ሚዛን አማን) ያሉ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት...ቅፈላህ ሲያምርህ ይቀራል... በሚል መንፈስ ተቃውሞአቸውን ገልፀዋል፤ ወጣቶችን ከሥራ አፋትቶ በሕልም ዓለም የሚያንሳፍፍ ይህ ወጣት ወደ ከተማቸው ድርሽ እንዳይል ለሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ተቃውሞአቸውን በደብዳቤ ገልፀዋል። የአማን ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ለሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ፀጥታና ሰላም ፅ/ቤት ጭምር በአባሪነት በላኩት ደብዳቤ ውስጥ ከሰፈረው የተወሰነው እንዲህ ይላል፦
" ሰው ጥሮና ግሮ የሰራውን የላቡን እንዲበላ፣ መፅሐፍ ቅዱስ ሲያስተምረን ሳለ፣ እነዚህ ኮንፍራንስ አድረጊ ወንድሞች በኢ-መፅሐፍቅዱሳዊ አስተምህሮ የተጠመዱ፣ አድራሻ ከማይታወቅ ምንጭ ብር ወደ አካውንታችሁ ይገባል እያሉ በስውር ዓላማ ትውልድ ሰርቶ እንዳይለወጥ በባዶ ተስፋ እንዲቦዝንና እንዲበዘበዝ የሚያደርጉ፣ በመንፈሳዊ አስተምህሮ ላይ ሳይሆን በገንዘብ ላይ ብቻ ያተኮሩ በመሆናቸው፣ ከዚህ
አስተምህሮ ጋር ተያይዞ ከወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት የተወገዙ በመሆናቸው፣ ይህን የማጭበርበር መንገድ ይዘው እንዳይመጡ ሕዝብ እንዳይበዘበዝ የከተማው ሰላምና ፀጥታ ከወዲሁ እንዲያስቆምልን ስንል በታላቅ አክብሮት እናመለክታለን።"
የብልፅግና ወንጌልና በሮንዳ በርን መፅሐፍ ውስጥ የተፃፈው የስበት ሕግ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። ልዩነታቸው በዋናነት ራሳቸውን የሚገልጡበት ሜዳ (conrext) ሊሆን ይችላል። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት በመንግስት መዋቅሮች ውስጥ እየተሰጠ ያለውን የስበት ሕግን በተመለከተ በአማን ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት የተወሰደው እርምጃ እጅግ አስተማሪ መሆኑን ማስመር ይቻላል።
ኢር. ጌታሁን ሄራሞ
የዛሬ 507 ዓመት፣ በዛሬዋ ዕለት፣ በኦክቶበር 31፣ 1517 አመተ እግዚ አንድ ብዙም የማይታወቅ መነኩሴ በአንዲት ትንሽ የጀርመን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮፌሰር የነበረ ሰው በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ በሚገኘው የቤተ ክርስትያን በሮች ላይ የተወሰኑ ወረቀቶችን ለመለጠፍ መዶሻ አነሳ። እነዚያን ወረቀቶች በቤተ ክርስትያን አደባባይ ላይ የለጠፈበት ምክንያት የቤተ ክርስትያኑ በር/አደባባዩ ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እንደ ማስታወቅያ ሰሌዳ ያገለግል ስለነበር በርከት ያለ ሰው እንዲመለከተውና ውይይት እንዲያጭር አስቦ ነበር።
በለጠፈው ወረቀት ውስጥ 95 አናቅጽት (Thesis) 'የኢንደልጀንስን' [indulgence] (የኃጢአት ይቅርታ ሰነድ) የመሸጥ ልምምድ ከጳጳሱ ፍቃድ ያገኘና አንድ ሰው 'ፑርጋቶሪ' [Purgatory] (ነፍስ ወደ ገነትም ሆነ ሲኦል ከመውረዷ በፊት የምትሆንበት ስፍራ) ውስጥ በምድር በሕይወት እያለ ስላጠፋው ስለሃጢያቱ የሚቆይበትን ጊዜ (ወደ መንግስተ ሰማይ ከመግባቱ በፊት) በሚገዛው 'ኢንደልጀንስ' መቀነስ ይችል ነበር የሚለውን ፀረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ የሚገዳደር ነበር። ይህ 'ኢንደንጀልስ' በወረቀት የሰፈረና የቤተ ክርስትያንን ይሁንታ አግኝቶ መግዛት ለቻለ ሁሉ የቀረበ ነበር። ህዝቡም ኢንደልጀንሱን ይገዛ ዘንድ 'በቅቤ አቅልጥ' ደላላ አሻሻጮች ይጎተጎት ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታዋን ሰጥታ ነበር። ህዝቡ ለራሱ፣ ለዘመዱና ለወዳጁ ይገዛ ነበር፤ በሞቱት ስም እንኳን ሳይቀር ይቸበችቡታል።
ሉተር 95 አናቅጽቱን ጽፎ ሲለጥፋቸው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ባሉት ፕሮፌሰሮች መሃል ውይይት እንዲፈጥር በማሰብ ነበር። ነገር ግን ዘጠና አምስቱ አናቅጽት ከቪተንበርግ ፕሮፌሰሮች ከባቢ በዘለለ በመላው የጀርመን ግዛቶችና በጠቅላላው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ዘንድ ታላቅ ሁካታን ለመፍጠር በቃ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ብዙ ህዝብ የዚህን መነኩሴ ስም ማወቅ ጀመረ፣ በቪተንበርግ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት ዶክተሩን ማርቲን ሉተርን።
ህዝብን በማወክና ባለመታዘዝ ቤተክርስትያን ከሰሰቸው፣ በጀርመን ንጉስ ፊትም ራሱን እንዲከላከልና ያደረገው ሃሰት መሆኑን አውቆ እንዲያስወግድ ታዘዘ። ያደረገው ስህተት መሆኑን ባለመቀበሉና ህሊናው ለቅዱሳት መጽሐፍት ተገዢነታቸውን በማጽናቱ ምክንያት የውጤቱን ስሜት 500 አመታትን ተሻግሮ ዛሬ እኛም ይሰማናል።
.
«ስቻለሁ የምለው አንዳች ነገር የለኝም፤ ኅሊናዬ ከሚያዘኝ ውጪ መሆን ትክክልም ሆነ አግባብ አይደለም። እነሆ፤ እዚሁ ቆሜያለሁ፤ ከዚህ ውጪ ምንም ላደርግም አይቻለኝም። እግዚአብሔር ሆይ እርዳኝ። አሜን።»
.
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንዳሉት፣ "አሕይዎና ተሐድሶ (Revival and Renewal or Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠ ሥርዐት (Establishement) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥዎ ካላቸው ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሐሳቦች ናቸው።" በዚህ ሰው ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በታማኝነት መታዘዝና መሰጠት ምክንያት የቤተክርስቲያን መልክ እንደ ቀደሞው ላይሆን ተለውጧል።
.
ተሐድሶ ብቻ መቆምን ይጠይቃል። ዘመንን መረዳትን፣ መጽሐፍትን መመርመርን፣ ለእግዚአብሔርና ለህሊናችን ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። ተሐድሶ ወደ አባቶችና አያቶች ለመንፀሪያ መመልከትን አንደ ቄንጥ አያይም። የድነትን መኸከለኛ፣ የእምነትን ፈፃሚ፣ የእግዚአብሔርን መገለጥ፣ ትምሕርተ ክርስቶስን አደብዛዥን ሁሉ ለመቃወም ሁለቴ አያስብም። ተሐድሶ ቃለ–እግዚአብሔር ማሕደረ–ክርስቶስ በተባለችው ቤተክርስቲያን ሲደፈጠጥ ጥሪውን በማማ ላይ ያሰማል፤ እነሆኝ ለህሊናዬም ለቃሉም ቆሜያለሁ ይላል። እግዚአብሔር ልጁን በገለጠበት ቃል በኩል ለኅሊናዬ ብቻዬን እንኳን ቢሆን እቆማለሁ የሚል እውነትና ፅናት ያድለን።
.
የዛሬ 507 ዓመት ግድም የተለኮሰውን የተሐድሶውን እሳት ከሰሞኑ አስበን ውለናል። ከተሐድሶው ቱሩፋቶች አንዱ የሆነውን የወንጌላዊው እምነትና የሕይወት ለውጥን አውስተናል። የተሐድሶው ውጤት ተራ የነገረ መለኮት ክርክር ሳይሆን ተግባራዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ግብርም ነው።
መልካም እለተ ተሐድሶ ማስታወሻ! የከርሞ ሰው ይበለን!
አማኑኤል አሰግድ
የ“ተሓድሶው ሲታወስ” መርኅ ግብር ዓላማ እንደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያችንን በመቃኘት ከየት እንደወደቅን ማስተዋልና መጠየቅን ማበረታት ነው። ቤተ ክርስቲያን ማንነቷንና (identity) ግብሯን (vocation) ካደበዘዙባት ባዕድ አስተምህሮዎችና ልምምዶች እንድትጠበቅ ውስጧን እንድትፈትሽ ማስቻል ነው። ጥቂት አበርክቶት ከሆነ።
እውነተኛ ተሓድሶ ጠያቂ ነው። ምዕመኑ የተነገረውን ሁሉ በቅን መንፈስ እንዲመረምር ያበረታታል። እንደ ቤሪያዎች “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን?” ብሎ መጠየቅ የተሓድሶ መለያ ባህሪ ነው። “አሜን”
ከማለት በፊት “ምን? ለምን? ና እንዴት?” እንድንል ያስታውሰናል። እስትንፋሰ መለኮት ያለባቸውን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደ ቱምቢ ዋቢ አድርጎ ይጠራል። የቅዱሱ መንፈስ ወደ እውነት የመምራት ችሎታም ዕውቅና ይሰጣል።
በመካከለኛው ዘመን በሮም ቤተ ክርስቲያንም የሆነውም እንደዚህ ነው ። በጊዜው የቅዱሳት መጻሕፍት ተደራሽነት በውስን የቤተ ክህነት ሰዎች አከባቢ ስለታጠረ የሰዎች ወግና ልማድ ከምንም በላይ ቅቡል ነበሩ። ስለ እምነታቸው የማያውቁና የማይጠይቁ ምዕመናን የሞሉበት ጊዜ ነበር። በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗ በብዙ መንፈሳዊና ሞራላዊ ዝቅጠት ውስጥ ገባች። የፖፑ ሥልጣን የኅጢአት ይቅርታ ሰነድ ሽያጭ ድረስ ደርሶ ነበር።
በመነኩሴው ሉተር ፈር ቀዳጅነት የተቀጣጠለው የተሓድሶው እንቅስቃሴ በጥያቄ ነበር የጀመረው። በዋናነት “የወደቀው የሰው ልጅ በቅዱሱ እግዚአብሔር ፊት እንዴት ሊጸድቅ (እና ሊቆም) ይችላል?” በሚል ወሳኝ ጥያቄ ። በርግጥ ጥያቄው ዐዲስ ነገር አላመጣም። ይልቁንስ ከነባሩ እውነት ላይ አቧራው እንዲራገፍና በጭጋጉ ላይ የቃሉ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ምክንያት ሆነ፤ ምስባኩን ለቃሉ ፍጹም ሥልጣን በማስገዛት ቀደሰ። ቤተ ክርስቲያንን ወደ እውነተኛ አምልኮና የወንጌል ተልዕኮዋ መለሰ። ከዚያም በኋላ በታሪክ ፈያጅ ጥያቄዎች ቤተ ክርስቲያንን ከእንቅልፏ እያባነኗት ወደ ትራኳ ሲመልሷት አንብበናል። ላቲኑ “Ecclesia reformata, semper reformanda” እንዲል!
በዘንድሮው የተሓድሶ ሲታወስ መርኅ ግብር “ወንጌላውያንና የሕይወት ለውጥ (Conversion)” ምንና ምን ናቸው ብለን እንጠይቃለን። ይህንን ማወቅስ እንደ ቤተ ክርስቲያን አሁን ከወደቅንበት ለመነሳት ፋይዳው ምንድነው ብለን እንወያያለን። ቅን ጥያቄ ባለበት በዚያ እውነተኛ ተሓድሶ (የግለሰብም የማኅበርም) ይሆናል። በዚህም መንገድ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ቀደመው መሠረቷ እየታደሰች (እየተመለሰች) ሙሽራዋን ትጠብቃለች ብለን እናምናለን።
ነገ (ጥቅምት 17) በ9፡00 ሰዓት
በካዛንቺዝ ዑራኤል መካነ ኢየሱስ እንገናኝ!
የወንጌላውያን ተሓድሶ እንቅስቃሴ
ፍጹማን ግርማ
sweet and bitter
ክርስቶስን መከተል ከፍቅር አባዜ ጋር ይመሳሰላል፣ ለዚያውም ድብን ያለ ፍቅር! መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን ተከታተሉ ሲል ከእኛ ከምንከተለው ትእዛዝ ተቀባይነት ባሻገር ፍቅር ራሱ የማስከተል አቅም ያለው በጎ ኃይል እንደሆነም ይነግረናል። ሰው ላፈቀረው የማይተወው ምን አለ? መልሱ ግልጽ ነው? “ምንም።”
ከምሩ ክርስቶስን የሚከተል አንዳንዴ በተመልካች እንደ እብድ ሊቆጠር ይችል ይሆናል። “ምነዋ” ቢሉት “እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው። ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤” 2ቆሮ. 5:13-14። ብሎ ይመልሳል።
ይህ ዓይነቱ እብደት ግን ከሴንሴሽናል ቅዋሴ ባሻገር የሚገኝ ለክርስቶስ የመሰጠት ህይወት ነው። ይገርማል ይሄን ያህል ነው ጌታውን የሚወደው? ሰውየው እብድ ነው፣ የሚያሰኝ የመገዛት የፍቅር ታዛዥነት ነው፣ አቅል አያስጥልም፣ ሙያ አያስወረውርም፣ ቀና መንገድን አያሳብርም፣ ነገር ግን ክርስቶስን በሚነድ ፍቅር ይከተላል። እውነተኛ ባልሆነ ፍቅር የሚከተል ሰው ከሚከተለው ከዚያ ሰው የግል አጀንዳ ይፈልጋል ያንን ባጣ ጊዜ ሽጦት ለመሄድ አቅም አለው። ምሳሌ ይሁዳ ነው
• ከዘላለም ብልጽግና ይልቅ ጊዜያዊውን ወደደ ከሌሎቹ ጋር ሲከተል ፍላጎቱ ድብቅ ነበረ፣ ጌታ ግን ያውቅ ነበር። ዝም አለው፣ በመሳም እስኪሸጠው ድረስ ታገሰው።
• ክርስቶስ እንደሚሰጥ ብቻ፣ ከሮም ቅኝ አገዛዝ ነጻ እንደሚያወጣ ብቻ፣ እንጀራ እንደሚያበላ ብቻ፣ እያሰበ ተከተለ፣ ዋጋ ክፈል ሲባል ከክርስቶስ ላይ ተሻምቶ ዋጋ ፈለገ፣ የማይሰጥ የሚቀበል ብቻ ተከታይ መጨረሻው “ነጋዴ” ነው፣ ያውም ፍቅርን - ተስፋዬ ጋቢሶ “ዘመኑ ፈጠነ ሮጠ ገሰገሰ” በሚለው መዝሙሩ “ዋጋ ክፈል ሲሉት ጥሎ ይፈረጥጣል” ያለው እንዲህ አይነቱን ነው።
• ይሁዳ የማስመሰል ሊቀጠበብት ነው፣ ሐሰተኛ ተከታዮች ያስመስላሉ፣ ገንዘብ፣ ክብርና ስልጣንን ይፈልጋሉ፣ ይህ ቢዝነሳቸው ነው፣ የኢየሱስ ስም ግን ቢዝነስ promotion ነው። አሁን በመካከላችን በአካል በእግሩ የሚራመድ ኢየሱስ የሚሸጥ የለም ይሁን እንጂ ከኢየሱስ ጋር የተነካኩ የቤቱን እቃዎች ጸሎትን በስሙ የሚደረግን ሁሉ በዋጋ ይሸጣሉ፣ እንዴት እነዚህ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች ይሆናሉ?
እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች በሕይወታቸው የደከሙትን ያህል ቢደክሙም ወድቀው በፊቱ ያለቅሳሉ፣ ይጸጸታሉ እንጂ፣ አይሸጡትም አይለውጡትም፣ አይጠቀሙበትም፣ ፍቅራቸው ጥልቅ ነው፣ በአንድ ምሽት የመከራ ክህደት የሚሰማቸው ጸጸት ሞቱን በሚመስል ሞት እስኪሞቱ ድረስ ፍቅር ይሰባቸዋል፣ ይመልሳቸዋል፣ ቢወቀሱ ይሰማሉ “መልስን እኛም እንመለሳለን ይላሉ”።
መጋቢ ሰሎሞን ጥላሁን
#ተሀድሶና_የአማኙ_ሁሉ_ክህነት!
የተሀድሶ በረከትና ...
🤔🤔
ቅድመ ተሀድሶ በመካከለኛው ዘመን ክርስትና "የቤተክህነት" (ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳት) ጥገኛ ነበር። የትኛውም ሰው ወደ ፈጣሪ፣ ክርስቲያኑም ወደ አምላኩ ለመምጣት፣ ለመለመን ሆነ ተቀባይነት ለማግኘት የነኚህ ሰዎች መካከለኝነት ያስፈልገው ነበር፣ አዳሾች በቃሉ ብቻ፣ ክርስቶስ ብቻ፣ ጸጋ ብቻ፣ እምነት ብቻ እና ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ መርሆች ላይ ባደረጉት እንቅሰቃሴ ወደ ብርሀን ከመጡት እውነቶች አንዱ የአማኙ ሁሉ ክህነት ነው።
እንደ መፅሐፍ ቅዱስ:- የብሉዩ ካህን መካከለኛነት ስራ በክርስቶስ ፍፃሜ በማግኘቱና፣ በእርሱ ሊቀ ክህነት አማኝ ሁሉ እንደ ካህን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ መቻሉ፣ ለእግዚአብሔር በመኖር እራሱን መስዋዕት አድርጎ ማቅረቡ፣ አምላኩን በምስጋናና በስጦታም ማምለኩ፣ ሌሎችንም በምልጃና በወንጌልም ወደ እግዚአብሔር ማምጣቱ አማኙን አዲስ ኪዳናዊ የካህናት ወገን ወይም ካህን ህዝብ አድርጎታል። (1ጴጥ2:5, 9፤ ዕብ13:15,16፤ ሮሜ15:15-16፤ ሮሜ12:1-3 ...)
ተሀድሶ ሁሉም በራሱ ቃሉን እንዲያነብ፣ በክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር እንዲመጣ፣ ሌሎች መካከለኞችን እንዲያስወግድና እራሱን እንደ አገልጋይ እንዲያይና እንዲያገለግል በማመቻቸት ለክርስትና ውለታ ውሎአል።
እንደ የትኛውም አፀፋ ሁሉ ይህ ለካቶሊካዊቷ ቤተክርስቲያን ባዕድ ትምህርትና ልምምድ የተሰጠው ምላሽ ችግሮች የሉበትም የሚባል አይመስለኝም። ከዚያም መሀል አንዱ የተደራጀውን ቤተክርስቲያናዊ ትስስር ወደ ብዙ ራስ ገዝ ቡድኖች መቀየሩ፣ ትላንት በቤተክርስቲያን ሰንሰለት ውስጥ አልፈው ለማስተማርና ለማገልገል ይለዩበት የነበረውን ስርአት አጥፍቶ ሁሉም በራሱ ቃሉን የሚተረጉምበት፣ ተጠያቂነት የሌለበት፣ በገባኝ፣ በተገለጠልኝ ስም ያለ በቂ ዝግጅት፣ ከቃሉና ከታሪካዊ እውነቶች የተፋቱ ትምህርቶች፣ ልምምዶች እንደ አሸን ሊፈሉ በቅተዋል። የአማኙ ሁሉ ክህነት እየተረሳም አዳዲስ መካከለኞች እየተፈጠሩ የማይፀልይ ፀላይ የሚፈልግ አፀላይ፣ በራሱ ቃሉን የማያጠና የአገልጋይ ጥገኛ (ስነመለኮት ተምረው የምሁር scholar ጥገኛ የሆኑ፣ ያከበሯቸውን ምሁራን "ያልተማረው" አማኝ "ለነቢዩ" ካለው ስፍራና መሰጠት ያልተናነሰ) መሰጠት ያላቸው ትውልድ እየተፈጠረ ነው፣ የሰው ጀሌ ሆነው የክርስትናቸውን ሚዛን የሳቱ "የነቢይ" "የሐዋርያና" "የፓስተር" "የምሁር" ጥገኞች ከክርስቲያኑ ማህበረሰብ አብዛኛው እየመሰሉ ነው።
እስከ ተሀድሶ ዘመን የዘለቀው አደረጃጀታዊም አንድነት የነበረው የቤተክርስቲያን ሕብረት ከተሀድሶ በዃላ እስከ አሁን ብዙ ሺህ ቤተእምነቶችና፣ የኑፋቄ ቡድኖች ወልዷል። በአማኙ ሕብረተሰብ መሀል ለመሰብሰብ የሚያስቸግር፣ ያልተዋቀረ የሁሉም አውቃለሁ፣ አገልጋይ ነኝ፣ ተገልጦልኛል፣ በማንም አልጠየቅም ባይነት ከሁሉም የክርስትና ጎራዎች የፕሮቴስታንቱ ጎራ መለያ እስኪሆን ተስፋፍቷል። በርዕሱ እንዳስቀመጥሁ በረከት የሆነው እውነት ችግር ሆኗል ማለት ቢታገለኝ ነው የተሀድሶ በረከትና ... ብዬ የተውሁት። የክርስትናን ማህበራዊነት ጥለናል።
አሁንም ሕብረትን የሚመልስ፣ አሰራርን የሚያስተባብር፣ ተጠያቂነት የሚያሰፍን፣ እንደልቡነትን የሚገታ ሌላ ተሀድሶ ካላገኘን የፕሮቴስታንቱ ክርስትና መሰነጣጠቅና ለማረምም ለማቅናትም የሚመች ትስስር ማጣት የከፋ ውድቀት መፍጠሩ፣ ከታሪካው ክርስትና ፍፁም ያፈነገጠ፣ የቃሉ ድጋፍ የሌለው አንግዳና ልዩ ሐይማኖት (ቶች) መሆናችን የማይቀር ይመስላል።
ተሀድሶን ስናስታውስ ተሀድሶ እየፈለግን።
የአማኙ ክህነት ማህበረሰባዊ ነው።
ከጥቂት ጭማሪ ጋር ድጋሚ የተለጠፈ
Pastor Tesfaye Gemechu
የ16ኛው ክፍለ ዘመን ተሐድሶው ሲጀምር
በኦክቶበር 31፣ 1517 ዓመተ እግዚ አንድ ብዙም የማይታወቅ መነኩሴ በአንዲት ትንሽ የጀርመን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮፌሰር የነበረ ሰው በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ በሚገኘው የቤተ ክርስትያን በሮች ላይ የተወሰኑ አናቅጽት የያዙ ወረቀቶችን ለጠፈ። እነዚያን ወረቀቶች በቤተ ክርስትያን አደባባይ ላይ የለጠፈበት ምክንያት የቤተ ክርስትያኑ አደባባዩ ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እንደ ማስታወቅያ ሰሌዳ ያገለግል ስለነበር ነው።
በለጠፈው ወረቀት ውስጥ 95 አናቅጽት (Thesis)ወይም አረፍተ ነገሮች ሰፍረዋል። የአናቅጽቱ ዋነኛ ትኩረትም ''የኃጢአት ይቅርታ ሰነድ'' ' [indulgence] የመሸጥ ልምምድ ከጳጳሱ ፍቃድ የተሰጠውና ሰው 'ፑርጋቶሪ'/[Purgatory] (ነፍስ ወደ ገነትም ሆነ ሲኦል ከመውረዷ በፊት የምትሆንበት ስፍራ) ውስጥ በምድር በሕይወት እያለ ስላጠፋው ስለሃጢያቱ የሚቆይበትን ጊዜ (ወደ መንግስተ ሰማይ ከመግባቱ በፊት) በሚገዛው 'ኢንደልጀንስ' መቀነስ ይችል ስለነበረ ነው። ይህ 'ኢንደንጀልስ' በወረቀት የሰፈረና የቤተ ክርስትያንን ይሁንታ አግኝቶ መግዛት ለቻለ ሁሉ የቀረበ ነበር። ህዝቡም ኢንደልጀንሱን ይገዛ ዘንድ 'ቅቤ አቅልጥ' የሆኑ አሻሻጮች ነበሩ። ህዝቡ ለራሱ፣ ለዘመዱና ለወዳጁ ይገዛ ነበር፣ ለሞቱት እንኳን ሳይቀር።
ሉተር 95 አናቅጽቱን ጽፎ ሲለጥፋቸው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ባሉት ፕሮፌሰሮች መሃል ውይይት እንዲፈጥር በማሰብ ነበር። ነገር ግን ዘጠና አምስቱ አናቅጽት ከዊተንበርግ ፕሮፌሰሮች ከባቢ በዘለለ በመላው የጀርመን ግዛቶችና በጠቅላላው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ዘንድ ታላቅ ሁካታን ለመፍጠር በቃ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ብዙ ህዝብ የዚህን መነኩሴ ስም ማወቅ ጀመረ፣ በዊተንበርግ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት ዶክተሩን ማርቲን ሉተርን።
ህዝብን በማወክና ባለመታዘዝ ቤተክርስትያን ከሰሰቸው፣ በጀርመን ንጉስ ፊትም ራሱን እንዲከላከልና ያደረገው ሃሰት መሆኑን አውቆ እንዲያስወግድ ታዘዘ። ያደረገው ስህተት መሆኑን ባለመቀበሉ ምክንያት የውጤቱን ስሜት 500 ዐመታትን ተሻግሮ ዛሬ እኛም ይሰማናል።
እነዚህ የተሐድሶው ማኮብኮብያ የነበሩት የተወሰኑ የወረቀት ቁርጥራጮች እንዴት ይህንን የሚያህል ትኩረትና ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ውጤት አመጣ ብሎ ማሰብ አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም የማርቲን ሉተር አስተምህሮ ከእሱ በፊት ከተነሱት ከነፒተር ዋልዶ፣ ጆን ዊክሊፍና ጆን ሁስን ከመሳሰሉ ተመሳሳይ አስተምህሮ ከሚከተሉት በላይ ገኖ የወጣበትን ምክንያት መጠየቅ ደግ ሳይሆን አይቀርም። ከሉተር መቶ አመት በፊት የነበረው ጆን ሁስ በተቃውሞ ምክንያት በእሳት ተቃጥሎ እየሞተ በነበረባት ሰዓት "በቀጣይ 100 አመት ውስጥ እግዚአብሔር አንድ ሰው አስነስቶ የማይቆም ተሐድሶን ያቀጣጥላል" ያለው ትንቢት ያለምክንያት አልነበረም።
ከላይ ላነሳናቸው ጥያቄዎች መልሱ የሚገኘው በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስትያንና ምዕራብ አውሮጳ የነበሩበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ነው። በ15ኛው ክፍለ ዘመን የተከወኑ ሁነቶች ተሐድሶ እውን እንዲሆን በር ከፋች ነበሩ። ሶስት መሠረታዊ ነገሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
የመጀመሪው የእውቀት ከቤተ ክርስትያን ቁጥጥር ውጪ መሆን ነው። የእውቀር መስፋፋት ቤተክርስቲያን በእውቀትና ትምህርት ላይ የነበራት ሙሉ ተጽእኖ እንድትነጠቅ አድርጓታል። በዚያ ላይ የማተሚያ ማሽን መገኘቱ እውቀት በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነበር። በርግጥ ተሐድሶው የተቀጣጠለው በታተሙ ወረቀቶች ነበር።
ሁለተኛው የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊዉ የሃይል ሚዛን ለውጥ ማድረጉ ነው። አውሮጳ የተለያዮ የንግድ መስመሮችን ያገኘችበትና ሃብት በብዛት ወደ መንግስታት የገባበት ወቅት ነበር። መንግስታት ከሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በላይ በለጠጋ በመሆናቸውና ሃብታቸውን ማጋራት ባለመፈለጋች ኢኮኖሚያዊ ቅራኔ ነበራቸው። ተሐድሶው የተራ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ብቻ ሳይሆን የገናና መንግስታትና የመሃከለኛ መደብ ልሂቃን ጥያቄ ጭምር በመሆኑ ስኬትን አገኘ።
ሦሥተኛው ምክንያት የቤተክርስትያን መሪዎች ከእረኝነት ይልቅ አምባገነን ገዢነታቸው ማየሉ ተሓድሶው እንዲሳካ መደላድል ፈጥሯል። ቤተክርስቲያን ትኩረቷን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይልቅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አድርጋ ነበር። በመንፈሳዊነት ስም ገንዘብ መሰብሰብ ባህልና ልማድ ሆኖ ነበር።
ስለዚህ…የነዚህን ምቹ አጋጣሚዎችን ስናይ እንዲያው ዝም ብሎ አጋጣሚ ሳይሆኑ መለኮት ቤተ ክርስቲያንን ከወደቀችበት ለማስነሳት ጽዋው እንደሞላ ያሳየናል። ነገሮችን እያሰናሰኘ ሁኔታዎችን እያስማማ ተሓድሶውን በትክክለኝ ጊዜ አምጥቷታል። ለዚህም ነው ይህ ተሐድሶ እግዚአብሔር በትክክለኛው ጊዜ ለቤተክርስትያን የላከው ነው የሚባለው። በዚህም ተሐድሶ ምክንያት እግዚአብሔር የመላ አለሙን ፊት ቀይሮታል።
የእኛም ዘመን የመላሸቅ ጥልቀት ተሓድሶን እንድንሻ የሚያደርገን ይመስለኛል። እኛም ተሐድሶ ያሻናል!
#ተሐድሶ
#ክርስትና
#የትሩፋን_ናፍቆት
አማኑኤል አሰግድ
ወርሃ ጥቅምት አድናቆትና ምስጋና ለአገልጋዮች የሚቀርብበት ወቅት ነው። ብዙ ዋጋ እየከፈላችሁ በቅንነት፣ በትጋትና በታማኝነት ለምታገለግሉ ሁሉ፣ እናመስግናለን። ከመጠነኛ እርማት ጋር በድጋሚ የቀረበው ይህ ጽሑፍ፣ እናንተን በማሰብና በመባረክ ነው። ዋጋችሁ ታላቅ ነው። ቡሩክ ሁኑ!
“በሲቃ ከማልቀስ በስተቀር ሕመሜ መታገሥ ከምችለው በላይ ሆኖብኝ በምሰቃይበት በአንድ ወቅት፣ ከጌታ ጋር ብቻ መሆን እንድችል በአጠገቤ የነበሩት ወገኖች ከክፍሌ እዲወጡልኝ ጠይቅዃቸው። ወዲያውኑ በልዑል እግዚአብሔር ፊት እንዲህ በማለት ልቤን ከእንባ ጋር
አፈሰስሁኝ፦
‘አንተ አባቴ ነኽ፤ እኔም ልጅህ ነኝ። አንተ እንደ መልካም አባት ሩኅሩኅና ቸር ነህ። መከራዬ መረዳት አልቻልሁም። ሆኖም በተመሳሳይ መከራ ልጄ ሲሰቃይ ባየው፣ እንደ ወላጅ አባት እያየሁ ዝም ማለት አልችልም ነበር። ይልቁንም ዕቅፍ አድርጌው አጽናናዋለሁ፤ ከመከራውም ሁሉ እንዲያርፍ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። ታዲያ አባቴ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊትህን ከእኔ ለምን ትሰውራለህ? እጅህንስ ለምን ታከብድብኛለህ? ፊትህን በመልካምነትህስ ወደ እኔ አትመልስምን?’”
ስፐርጀን ይቀጥላል፦
“እናም ይህን ስቅዩ ልቤን በእግዚአብሔር ፊት ካፈሰስሁ በኋላ፣ ውስጤን ሰላም ሞላው። ወገኖች ተመልሰው ወደ ክፍሌ ሲገቡ፣ ‘እግዚአብሔር የጭነቅት ጩኸቴን ሰምቶአል፤ ሕመሜም ቀሊል ሆኖአል። እግዚአብሔርን እባረካለሁ’ አልኋችው።” (C. H. Spurgeon, Heaven’s Nurse Children, Metropolitan Tabernacle, Newington)
በመንፈስ ቅዱስ ኀይል የቃሉን ብርሃን በሚገልጠው ስብከተ ወንጌሉ እስከ ዛሬ ድረስ የሚወሳው እንግሊዛዊው ቻርልስ ሀደን ስፐርጀን (19 June 1834 – 31 January 1892)፣ አገልግሎቱ በብዙ መከራና የልብ ስብራት የታሸ ነበር። ከመርዛም ስም ማጠልሽት፤ ዐጥነት ከሚሰብር ትችት፤ ከልዝብተኛ ጋዜጠኞች የማያቋርጥ አቃቂር፤ ከአስቸጋሪ መሪዎች ጋር ማገልገል፤ ምንም ቢደረግላቸው ከማይረኩ አባላት ክፉ አንደበት፤ በቅርብ ወዳጆች ከመከዳት፤ እንዲሁም ምክንያት ከሌለው ድባቴ (causeless depression) ጋር እየታገለ ነበር የሚያገለግለው።
በስኬትና ድል መካከል ስለሚያልፈበት ነውጥ ደግሞ እንዲህ ይላል፦
“ዛሬ ሆሳዕና በማለት ስሜን ያገነነው ያው ሕዝብ፣ ሊሰቅለኝ . . . ያመንሁት ሲከዳኝ፣ እጁን የሰጠኝ ሲነሣኝ፣ በእጅጉ ያማል። ከልብ ስብራት የተነሣ፣ ከቅንድቤ ላብ እስኪንቆረቆር ድረስ ብዙ ጊዜ የስም ጉድፈት ዶፍ ወርዶብኛል፤ በጥልቅ ሐዘን የተሰበረው ልቤ ለመቆም ዐቅም አሳጦቶ ብዙ ጊዜ አንበርክኮኛል። በእግዚአብሔርም ፊት ተደፍቼ አልቅሼአለሁ። እነዚህን ነውጦች መታገሥ የምችልበት የእግዚአብሔር ጸጋ አልተለየኝም። ከሁሉም በላይ የሚከብደኝ ጌታ ፊቱን ያዞረና ዝም ያለኝ ሲመስለኝ የሚከበኝ የቀን ጨለማ ነው። ሆኖም በመከራ ብዛት የእኔ ብርታት ሲሟጠጥና የጌታ ጸጋ ሲትረፈርፍ፤ አንዲሁም በብቸኝነት ቁር ውስጥ የእርሱ አብሮነት ዐቅም ሲሆነኝ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ . . . ። (Salvation of the Lord, Jonah 2:9 - May 10, 1857, New Park Street Pulpit Volume 3).
በቅንነት ያገለገለበት የመጥምቃውያን ማኅበር ያለ ፍትሕና ስለንጽሕናው መሟገት እንዳይችል በማድረግ በአደባባይ አዋርዶ ሲያሰናብተው፣ አገልግሎቱ አንዴ በዝና ተራራ ላይ ከፍ ሲያደርገው፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ መውጫ የሌለው የውርደትና የስብራት ሸለቆ ውስጥ ሲከተው፣ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ የነበረው ሙሉ እምነትና ለክርስቶስ የነበረው ፍቅር ዐቅም ሆነውታል።
በአገልግሎቱ ማብቂያ ገደማ፣ ሁለት የተቀናጁ ሴራዎች እጅግ ጐድተውት ነበር። አንደኛው፣ “The Down-Grade Controversy of 1887–88 ” (የዝቅታ ወይም የቁልቁሎሽ ውዝግብ) በመባል የሚታወቀው ሁለት ዓመት የፈጀና ሥጋዊነት የለበሰ የመጥምቃውያን ማኅበር አድካሚ ስብሰባ ነበር። ወቅቱ የቻርልስ ዳርዊን ሳይንሳዊ ፍልስፍና ለልዝብ/ልቅ ነገር መለኮት (theological liberalism) ዘር በመሆን፣ የወንጌላውያኑን መሠረታዊ የእምነት ፋይዳዎች መሸርሸር የጀመረበት ነበር። በተለይም ሁለት ዐበይት ክርስቲያናዊ እውነቶችን ፈተና ውስጥ ነበሩ። አንደኛው፣ የመጸሕፍ ቅዱስን የበለይነት፣ ሕጸጽና (infallible) ግድፈት አልባነት (inerrant) በተመለከተ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የወልድን መለኮታዊነት እንዲሁም ምትክ ቤዛዊ ሞቱን በተመለተ ነበር። ስፐርጀን የነበረውን ስጋት በግልጽ ተናግሮ ነበር። ከዚያም አልፎ፣ ውዝግቡ እርሱ በሚመራ ወርሃዊ መጽሔት ላይ በመታተሙ፣ ወደ ልቅ ነገር መለኮት ማዘንበል በጀመሩና ቀደም ሲለም ከእርሱ ጋር የሻከረ ግኑኙነት ከነበራቸው መሪዎች ጋር የከረረ ግጭት ውስጥ ከትቶታል።
ሁለተኛው ደግሞ፣ “የባሪያን ንግድና አሳዳሪነት” አስመልክቶ የነበረውን አቋም ፓለቲካዊ ይዘት እንደነበረው ተደርጐ የተነዛው የሐሰት ውንጀላ ነበር። ከዚህም የተነሣ ስብከተ ወንጌሎቹ በምድረ አሜሪካ እንዳይሰራጩ፣ እንዲሁም ተደማጭነት እንዳይኖራቸው፣ በደቡባዊ መጥምቃውያን ማኅበር ውስጥ የስም የማጥፋትና የአቅላይነት ዘመቻ ይካሄደበት ነበር።
የልቅ ነገር መለኮትን መብቀልና የሥነ-ምግባር ዝቅጠትን በተመለከተ፣ የነበረውን ሐዘን እንዲህ በማለት ገልጾአል፦
“የከተማችን ለንደን መንገዶች በበደልና በክፋት ተሞልተዋል፤ ብቅ ማለት ለጀመረው እምነት የሌሽነት እያሳየን ያለው ዝምታ (ባይተዋርነት) ያሳስበኛል. . . ያልተቀደሰች ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር ፈጽሞውኑ መኖርያው አያደርግም፤ በሥጋዊነት የተዥጐረጐረን ሕይወት እግዚአብሔር ይጸየፋል።” (The Best War-Cry, March 4, 1883)።
“የባሪያን ንግድና አሳዳሪነት” አስመልክቶ ደግሞ፣ “ከውስጥ ነፍሴ እጅግ አብዝቼ የምጠላው ነው . . . ከተለያየ እምነት ለሚመጡ [ክርስቲያኖች] የጌታን ራት አካፍያለሁ፤ ኾኖም ከባርያ ነጋጅና አሳዳሪ ጋር ፈጽሞውን ምንም ዐይነት ኅብረት አይኖረኝም።” በማለት በወቅቱ የነበረውን መዋቅራዊ ዘረኝነት ፊት ለፊት ተጋፍጧል። (The Christian Watchman and Reflector, Boston Baptist Newspaper, January 26, 1860)
በመጨረሻም በአደባባይ፣ የቤተ ክርስቲያንን ኅብረት እንደማይወድና እንደማይታዘዝ ተቆጥሮ ከኅብረቱ እንዲሰናበት ተደርጐአል። መገለል፣ የቅርቤ ናቸው ያላቸው ወዳጆቹን ማጣት፣ ብቸኝነቱና የስም ማጥፋቱ ዘመቻ ውስጡን እጅግ ጐድተውታል። በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ የአገልግሎት ውጣ ውረድ ውስጥ እምነቱ ጽኑ ነበር፤ “To pursue union at the expense of truth is treason to the Lord Jesus . . . He is our Master and Lord, and we will keep his words: to tamper with his doctrine would be to be traitors to himself.” (እውነትን መስዋዕት ያደረገ የአንድነት ፍለጋ፣ ክርስቶስን መካድ ነው . . . እርሱ መምህራችንና ጌታችን ነው፤ ቃሉን እንጠብቃለን፤ የእርሱን አስተምህሮ መነካካት እርሱን እራሱን መካድ ነው።” ("A Fragment Upon the Down-Grade Controversy, Sword and Trowel, November 1887)
ስለመገፋቱ ደግሞ፦
ቅዱስ ቃሉን የመተርጎም ዋጋ: ዊልያም ቲንዴል
..
ከዛሬ 487 ዐመታት በፊት በዛሬው ዕለት መጽሐፍ ቅዱስን ከላቲን ወደ እንግሊዘኛ በመተርጎሙ ምክንያት በአደባባይ በቋሚ እንጨት ታስሮ ዊልያም ቲንዴል እንዲቃጠል ተደረገ። ቅዱሱን መጽሐፍ በአገሬው ቋንቋ ስለተረጓመ ብቻ በአደባባይ ጭካኔያዊ ግድያን ተገደለ። እጃችን ላይ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ እጃችን ላይ እንዲገባ ብዙ ሰማዕትነት ተከፍሎበታል።
ዊልያም ቲንዴል መጽሐፍ ቅዱስን ከዋናው እብራይስጥና ግሪክ ቋንቋ ወደ እንግሊዝኛ በመተርጎሙ ምክንያት ለእስር፣ ለእንግልትና መከራ ተዳርጓል። በወጣትነት እድሜው ታዋቂ የኦክስፎርድ ተመራማሪና የነገረ መለኮት ሊቅ ሆኖ ከመኖር ይልቅ የበራለትን የቅዱሱን ቃል እውነት ለሁሉም ለማሳወቅ ሲል ተሳዳጅ ሆነ። የማይነቀነቀውን የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስልጣንን ቃሉን ሁሉም እንዲያነበውና ወደ ጸጋው እውነት እንዲመለስ በማለት በቅዱሳት መጽሐፍ ትርጓሜ ነቀነቀው። በዚህም ምክንያት በ30 ዐመቱ የሞት ፍርደኛ በመሆን ወደ ቤልጀም ተሰደደ። ስደቱ መከረኛና እስር የበዛበት ነበር። በዚያም ውስጥ ሆኖ ግን ትርጉሙን ከማጠናቀቅ ወደ ኋላ አላለም።
ለአስራ ሁለት ዐመታትም በስደት ከተንገላታ በኋላ በዚህ እለት (6 October 1536) ብራሰልስ ከተማ አደባባይ ላይ በቁሙ በእሳት አጋይተውት በ41 ዐመቱ አንቀላፋ።
#ተሐድሶው
#ዊልያም_ቲንዴል
በአማኑኤል አሰግድ
የቅይጣዊነት ጣጣ
የተደናበረው የካውንስሉ መግለጫ እና የከሸፈው የህብረቱ መግለጫ
በበርካቶች ዘንድ የወንጌላዊው ክርስትና መሰረታዊ ችግሮች ተብለው የሚቀርቡት ሶስት ችግሮች ናቸው። እነርሱም የስህተት ትምህርት፣ የስህተት ልምምድ እና የአመራር ቀውስ ተብለው ከእነትንታኔያቸው ይቀርባሉ። እኔም እስማማለሁ። እነኚህ ሶስቱም ችግሮች በወንጌላዊያን መካከል በሰፊው የሚታዩ ቤተክርስቲያንን እያደቀቋት የሚገኙ ችግሮቻችን ናቸውና። ነገር ግን በእኔ ግምጋሜ መሠረት የወንጌላዊያኑ አብያተክርስቲያናት መሠረታዊ ችግር "ቅይጣዊነት" ነው።
ምክንያቱም "ቅይጣዊነት" በግና ተኩላውን በአንድ ጎረኖ ስለሚያሳድር ስህተቱን እና አሳቹን ነጥለን እንዳንመታው የሃሳዊያን መሸሸጊያ ጫካ ሆኖ ያገለግላልና።
መቼም የስህተት አስተምህሮንም ሆነ የስህተት ልምምድን በምድር ላይ እንዳይኖሩ ማድረግ አይቻልም። መፅሐፉም "ሃሳዊያን ይበዛሉ" ገናም ደግሞ "ሃሰተኛው ነቢይና ሃሰተኛው ክርስቶስ" ተገልጠው ብዙዎችን ያስታሉ ብሎ አስቀድሞ ነግሮናል። ሃሳዊያንን ማጥፋት ፈፅሞ አይቻልም። ለቤተክርሰሰቲያንም ሃሳዊያንን ከምድረ ገፅ እንድታጠፋ ተልዕኮ አልተሰጣትም። አልታዘዘችም።
ነገር ግን የክርስቶስ የሆነችው ቤተክርስቲያን ከሃሳዊያን እንድትርቅ እና አሳቹን ከመካከልዋ እንድታርቅ መመሪያ ተሰጥቷታል። ከቅይጣዊነት ራሷን እንድትጠበቅ ግዴታዋ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በመልዕክቱ ከሃሳዊያን ጋር ሊኖረን ስለሚገን ግንኙነት ሲነግረን "ሰላም አትበሉዋቸው" የሚል ጠንካራ ትዕዛዝ አስተላልፏልና። መፍትሔውም ይኸው ብቻ ነው።
በሰሞነኛውም የሃሳዊው ኡበርት ኢንጀሰልስ ወደ ሀገራችን መምጣት ሰበብ በግልፅ የተመለከትነው ወንጌላዊቷ ቤተክርስቲያን "በቅይጣዊነት" ፈተና እየተናጠች መሆኑን ነው። የካውንስሉ የተደናበረ መግለጫ እና የህብረቱ የከሸፈ መግልጫም የዚሁ ማሳያ ነው። ወገኖች፤ የወንጌላዊያኑ መሠረታዊ ችግር "ቅይጣዊነት" ነው።
የካውንስሉ መደናበር
ካውንስሉ በግና ተኩላውን በአንድ የቀላቀለ የወንጌል ጠላት የሆነ ተቋም መሆኑ የተገለጠ ነው። በአባሉቱም ሆነ በአመራሩ መካከል "ሃሳዊያኑ" ቀዳሚ ተሰላፊዎች ናቸው። ኡበርትን ወደ ኢትዮጵያ ያስመጣውም ግለሰብ ሆነ የሚመራው ተቋም የካውንስሉ አባላት ናቸው። መርሃ ግብሩም የተከናወነበት አዳራሽ በካውንስሉ አባል ባለቤትነት የሚተዳደር ነው። በመርሃ ግብሩ ላይም ፊት ወንበር ላይ መደዳውን የተሰለፉት የካውንስሉ አባላት ናቸው። የተጋበዘው ሰባኪ ደግሞ ቀንደኛ ሃሳዊ ነው። በአንፃሩ ደግሞ የካውንስሉ አባል አብያተክርስቲያናት መካከል በርካቶቹ ቀደምትና (Main line) "ጤነኛ ነን" የሚሉ አብያተክርስቲያናት ናቸው። በክፉ ቀን ከሃሳዊያን ተቀይጠው።
ታዲያ ለካውንስሉ የተደናበረ መግለጫም ሰበብ የሆነው ይኸው "ቅይጣዊነት" ነው። ካውንስሉ፤ ዝም እንዳይል "ጤነኛ" የተባሉትን አባላቱን ሊያስከፋ ሆነ። እንዳይቃወም ከአመራር ጀምሮ በውስጡ የተሰገሰጉትን ሃሳዊያን ሊያበሳጭ ሆነ፤ እና ምን አደረገ? ማህተም፣ ፊርማ እና ቲተር የሌለው የተቃውሞ መግለጫ አውጥቶ በገፁ ላይ ለጠፈ እና ከሰዓታት በኋላ አወረደዋ። መደነባበር.....። የቅይጣዊነት ጣጣውም ይኸው ነው። "ሃሰተኛ!" ብለህ የፈረጅኸው ሰው አባላቶቼ (ጓዶቼ) ባልሃቸው አጃቢነት እየተሞገሰ ሲቆም እና የምታደርገው ሲጠፋህ ማለት ነው። "ላም እሳት ወለደች...." ይል የለም ተረቱ?
የህበረቱ ክሽፈት
የወንጌላዊያን አብያተክርሰሰቲያናት ህብረት ከሽፏል። ምክንያቱም በካውንስሉ ላይ "ካውንስሉ የሃሳዊያን ክምችት ነው" ሲል እና መግለጫ ሲያወጣ ከርሞ ካውንስሉ ምንም ዓይነት የአሰራር ለውጥ ባላሳየበት ሁኔታ ከዕለታት በአንዱ ቀን ድንገት ብድግ ብሎ (ወይም ከሆነ አካል ትዕዛዝ ተሰጥቶት ሊሆን ይችላል) "በወንበር ተደራድሮ" የካውንስሉ አባል እና "አብሮ ሰር" መሆኑን ነግሮናልና። የቅይጣዊነቱም ሰለባ ሆኗልና።
ከሰሞኑም ከኡበርት ኢንጅልስ መምጣት ጋር ተያይዞ ባወጣው መግለጫም የታየውም ህብረቱ የቀድሞ ቁመናውን ያጣ መሆኑን ነው። ዋንውን ሰው "ጋባዡን" ትቶ "ከኡበርት ተጠበቁ" የሚል የከሸፈ መግለጫ አውጥቷልና። ምክንያቱም ህብረቱ ሚራክል ተካ ላይ መግለጫ ቢያወጣ ከካውንስሉ ጋር ስለሚጣላ ፈርቶ ነው (የካውንስሉ ዋና ዋና ሰዎች መርሃ ግብሩ ላይ ታድመዋልና)። ቅይጣዊነት ጣጣው ይሄ ነው።
ቅይጣዊነት የአሁኗ ዘመን ወንጌላዊቷ ቤተክርስቲያን ዋነኛ ፈተና ነው። ምክንያቱም ከላይ እንደጠቀሰሁት:-
"ቅይጣዊነት" በግና ተኩላውን በአንድ ጎረኖ ስለሚያሳድር ስህተቱን እና አሳቹን ነጥለን እንዳንመታው የሃሳዊያን መሸሸጊያ ጫካ ሆኖ ያገለግላልና።
ቴዎድሮስ ተጫን
መንፈቅ ያልሞላው ወግ . . .
እኔን በጣሙን የሚያሳስበኝ፣ እጅጉን የሚያሳስበኝ ነገር "ነብይ"፣ "ሐዋሪያ"፣ "አገልጋይ"፣ "ፓስተር"፣ ምናምን ተብለው ሐሰት ከሚቀፈቅፉ፣ ፍቅረ-ንዋይ-መር ከሆኑና በፕሮቴስታንት ስም ከሚንቀሳቀሱቱ ይልቅ ነባሮቹ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያናት ናቸው፤ ደግሞም እኛ በውስጣቸው ያለነው "አገልጋዮች" ነን፡፡ ሁለት ምክንያቶችን ለጊዜው ማንሳት በቂ ይሆናል . . .
(1) ለመሆኑ ባሳለፍናቸው ደርዘን በማይሞሉ አሠርት ዓመታት ውስጥ ምን ብንሰብክ፣ ምን ብናስተምር፣ ደግሞም እንዴት ብንደራጅ ነው ለእንደዚህ ዓይነት ወሮበላ "አገልጋዮች" አልፎ የተሰጠ ምዕመን ልናፈራ የቻልነው?? ለነገሩ ይህ አገራዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን ዓለማቀፋዊም ጭምር ነው፡፡
(2) ርዕስ ወዳደረኩት መንፈቅ ወደማይሞላው ወግ ልውሰዳችሁ፡፡ ከነባር አብያተ ክርስቲያናት ባንዲቷ ቤ/ክ ውስጥ በ"ፕስትርና" "የሚያገለግል" ("የሚተዳደር" ብለው ደስ ይለኝ ነበር!) ካንዱ ጋር በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተን ስንጫወት እንደርሱ ያሉ አገልጋዮች ከሚጠበቅባቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች መካከል አንዱ አማኞችን ወደሙሉ መረዳት ማምጣት እንደሆነ ስነግረው በፍጥነት አቋረጠኝና እስካሁን የሚያስደነግጠኝን ነገር ተናገረ (የያኔው ድንጋጤ እስከዛሬ ይነዝረኛል!)፡፡ እናም እንዲህ ነበር ያለኝ፦ "ሕዝብማ እንዲያውቅ አናደርግም! ካወቀ አያስቀምጠንማ! አሁን እንኳን አልቻልነውም!"
እና ይህን መርህ የሚከተል "ፐስታሪ" (ጥቂት ነው ብዬ ራሴን ለማታለል አልሞክርም) ምን ዓይነት ምዕመናን ሊያፈራ እንደሚችል አስቡትማ! ያለምንም ጥርጥር የእውነትን ቃል ሕዝባቸውን ለማስታጠቅ የሚተጉ፣ የሚደክሙ፣ የሚለፉ፣ ለዚህም ቀላል የማይባል ዋጋ የሚከፍሉ አሉ፡፡ ይሁንና መድረኮቻችንን፣ ምስባኮቻችንን ብንመለከት የእንደነዚህ ዓይነት ድንቅ እረኞች ድርቅ የተመቱ ናቸው፡፡ ይልቁንም ከመልዕክታቸው ይልቅ ድምጻቸው በጎላ፣ ከሕይወታቸው ይልቅ ጩኸታቸው በሚሰማ፣ ብንጠጋቸው የሚሰቀጥጡ "ፐስታሪዎች" "ተባርከናል"፡፡
እና ጩኸትን ያስለመዱት ምስኪን ሕዝብ ጩኽት ፍለጋ ቢሄድ፣ ውኃ የሌለባቸውን ደመናዎችን ተስፋ አድርጎ ቢሄድ ምን ይፈረድበታል፡፡
ሁላችንም ራሳችንን አንመልከት! ቤታችንን እንመልከት! እንዴት እንደሰራን እንዳለ ራሳችንን እንፈትሽ፡፡ ይህንን ስናደርግም "ነብይ"፣ "ሐዋሪያ"፣ "አገልጋይ"፣ "ፓስተር" እየተባሉ የስህተትን እንቁላሎችን ጥለው፣ ስህተትን የሚቀፈቅፉቱንም "ሃይ" እንበል!
ልደቱ አለሙ (ዶ/ር)
በስምምነቱ መሠረት ባለደርሻ አካል አገራት፣ የጾታ ማንነትን፣ የወሲብ ጤንትንና ውልጃን አስመልክቶ፣ ነጻና ሙሉ የሆነ የጤና አገልግሎት እንዲኖራቸው፤ አንዲሁም በተመሳሳይ ጕዳዮች ላይ የዩኔስኮን “የተሟላ የጾታ ትምህርት መመሪያ” ተግባራዊ እንዲከተሉ ይጠይቃል። (አንቀጽ 40፤ ቍ. 6) አገራት ይህን የምዕራቡን ዓለም “የጾታ” ትምህርት የሥርዐተ ትምህርታቸው አካል እንዲያደርጉ ኅብረቱ እርዳታ ያደርጋል። ይህ ብዙ አስከፊ እንድምታ አለው። የዩኔስኮ ትምህርት ራሱ የተቀረጸው የምዕራቡን ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም ታስቢ በማድረገ ነው። ለአብነት ያህል አንድ ማስረጃ ብቻ ልጥቀስ፦
“ወሲባዊ ማንነት ማኅበራዊ ውቅር ነው። ውስብስብ፣ በወቅትና በሁኔታ ተለዋዋጭ ሲሆን፣ በግለሰቦች ልምምድ፣ ሃይማኖታዊ፣ በባህላዊና ማኅበራዊ እሴች ይወሰናል . . .በዚህ ረገድ ልጆች በተለያየ የሕይወት ደረጃቸው ጤናማና ኀላፊነት ያለው ውሳኔ እንዲወስኑ ትምህርት እጅግ አስፈላጊ ነው . . . ‘የተሟላ የጾታ ትምህርት’ (CSE) ዓላማ፣ ልጆች በየትኛውም መንገድ ደስታና ርካታ የሚሰጣቸውን ‘ጤናማ’ የወሲብ ልምምድ ‘ነጻነታቸውን ‘በአገባቡ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ዕውቀት መስጥት ነው።”(International Technical Guidance on Sexuality Education (ITGSE, Conceptual Framework for Sexuality in the Context of Comprehensive Sexuality Education (CSE)፡ The Global Education 2030 Agenda፣ p.17-18, UNESCO, 2018).
ይኸው የዩኔስኮ መመሪያ ልጆችን በዕድሜ ከ 5-8፤ ከ 9-12፤ ከ13-15 እንዲሁም ከ 15ዓመት በላይ በመከፋፈል የምዕራቡን ዓለም የጾታ ትምህርት በርዝር ያቀርባል። ልጆች ከአምስት ዓመታቸው ጀምሮ “ጾታ ማኅበራዊ ውቅር” እንጂ በተፈጥሮ (ባዮሎጂ) የተወሰነ ያለመሆኑን እንዲማሩ ይደረጋል። ከ12 ዓመት በላይ የሆኑት ደግሞ የጾታ ዝንባሌና አገላለጽን (gender identity/norms/expressions) ማስተናገድ፣ የጾታ ዝውውር፣ እርግዝናን የመከላከያ መንገዶች፣ ደስታ እሰከተገኘበትና ‘ጤናማ’ እስከሆነ ድረስ በየትኛውም መንገድ የግል የወሲብ ፍላጐት የማረካት ነጻነት እንዲሁም የሴት ልጅ የውርጃ መብትን በተመለከተ ይማራሉ። (ITGSE, The Global Education 2030 Agenda , “The Social Construction of Gender and Gender Norms”, 50-72).
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ካውንስል በ June 30, 2016 ባሳለፈው ውሳኔ (A/HRC/RES/32/2) መሠረት መንግሥታቱን የሚያማከር የሙሉ ጊዜ “የወሲብ ዝንባሌና የጾታ” አጀንዳ (Sexual Orientation and Gender Identity - SOGI) አማካሪ አለው። በተመሳሳይ መልኩ፣ የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች (UN-Women) ዓለም ዐቀፍ የጾታ እኩልነት አጀንዳ ተፈጻሚነት እንዲኖረው የሙሉ ጊዜ አማካሪ (“Dedicated LGBTIQ+ Rights Specialist) አለው። የመንግሥታቱ ሴቶች ቢሮ ባወጣው መመሪያ መሠረት “በተለምዶ ጾታን ‘በወንድነትና በሴትነት’ በመክፈል የሚበይነው ዕይታ አባዊ (patriarchal) እና ወግ ተከተል (heteronormative) በመሆኑ መጋፈጥ ያስፈልጋል” ሲል ይሞግታል። በዚሁ መሠረት “ተፈጥሮአዊ ጾታ (biological sex) የሚለው አሰያየም፣ የጾታ ለውጥ ያደረጉ ሰዎችን ለጾታዊ ኢፍትሐዊነት፣ አድሎአዊነትና አግላይነት አሳልፎ ስለሚሰጥ የእነርሱን “የጾታ ማንነት” የሚያካትትና ዐቃፊ የሆነ ሌላ ተጨማሪ የመገለጫ ስያሜ ያስፈልጋል” የሚል መመሪያ አለው። (LGBTIQ+ Equality and Rights Internal Resource Guide, UN Women, 2022).
4) የቃላት ዐውዳዊ አረዳድ ልዩነትና የስምምነቱ አሳሪነት
በሚከተሉት መረዳቶች ላይ፣ ሙሉ ለሙሉ በሚያሰብል ሁኔት፣ የኢትዮጵያ (በእኔ ግምት የአብላጫው የባለ ድርሻ አካል አገራትን ጨምሮ)፣ ከምዕራቡ ዓለም መረዳት ጋር ተቃራኒ ነው። ይህ ስውር ደባ ነው። ዋና ዋናዎቹን ላንሳ፦
• Gender (ጾታ) – 61 ጊዜ የተጠቀሰ
• Gender equality (የጾታ እኩልነት) – 28 ጊዜ የተጠቀሰ
• Inclusive/inclusiveness (አካታች/አካታችነት) –103 ጊዜ የተጠቀሰ
• Sex/Sexual (ወሲብ./ወሲባዊነት) - 33 ጊዜ የተጠቀሰ
• Universal health coverage / access to reproductive health – (ሁሉን ዐቀፍ የጤና ሽፋን) - በአንቀጽ 29 “ጤና” የሚለው ክፍል የተካተተና ለውርጃ፣ ላልተገደበ ወሲብ፣ ለጾታ ዝውውርና ተያያዥ ቀውሶች በር ከፋች ውል።
• Hate speech/ discrimination/ advocacy of hatred/ discriminatory practices (የጥላቻ ንግግች፣ አግላይ ተሟጋችነት) - 45 ጊዜ የተጠቀሰ ሀሳብ - ለወንጌል መልእክት፣ በተለይም የክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነት መናገር፤ የጋብቻን ክቡርነት፤ ጾታና ወሲብ፤ ውርጃና ተመሳሳይ መጸሐፍ ቅዱሳዊ ዕይታዎችን ማስተማር እንደ “ወንጀል” የሚታይ ያደርጋል። በእነዚህ መሠረታዊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ላይ በምዕራቡ ዓለም ያለቸው ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ፈተና ውስጥ እንዳለች ልብ ልንል ይገባል።
የዚህ ስምምነት ሕጋዊ አሳሪነት የባልደርሻ አገራትን ሉዓላዊነት የሚሸረሽር ነው። እጅግ አሳሳቢው አገራት ስምምነቱን በዓለም ዐቀፍ መድረኮች የማስፈጸም ግዴታ እንዳለባቸው ስምምነት መደረጉ ነው (አንቀጽ 6፤ ቍ. 3፤ አንቀጽ 88፤ ቍ. 5)። ልብ እንበል፤ ይህ ስምምነት 27 የአውሮፓ አንዲሁም 79 የአፍሪካ፣ የካሪቢይ እና የፓሲፊክ፣ በድምሩ 106 አገራት በሥራቸው ያለውን ወደ ሁለት ቢሊዪን ሕዝብ የሚወክል ነው። ይህም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካለው ወንበር ከግማሽ በላይ ማለት ነው። በስምምነቱ ላይ የተዘረዘሩት ጕዳዮች ሁሉ ባለድርሻ አካላት፣ በአገር፣ በአኀጉርና በዓለም ዐቀፍና መድረኮች (ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታታት) ላይ የማስፈጸም (adoption of common positions on the world stage) ግዴታ ይኖራቸዋል። በዝምታ የድምፅ ተዐቅቦ ወይም በተቃውሞ ረድፍ መቆም አይቻልም። (አንቀጽ 1፣ “ዓላማ”)።
5) ማኅበራዊ መገናኛዎች ዐቃፊ፣ አካታችና “ጾታ ደጋፊ” እንዲሆኑ የሚዲያ ፓሊሲዎችን ማስረጽ - Gender Mainstreaming
በተደጋጋሚ የሚነገር “እንግዳ ዐሳብ” እያደር ተቀባይነት እንዲሚኖረው እናውቃለን። የምዕራቡ ዓለም ባህል ምን ያህል በትውልዳችን ላይ ተጽእኖ እንዳለው የምንገነዘበው ሐቅ ነው። እውነትና ግብረገባዊነት አንጻራዊ የሆኑበት፤ እንዲሁም፣ ሁሉ ዐቃፊነትና አካታችንነት የሰለጠኑበት ዘመን ነው። ይህ ስምምንት “መቻቻልና መቀበበል፣ አካታችና ዐቃፊ” በሚሉ እስቤዎች፣ የማኅብረሰብን ሃይማኖታዊ እሴቶች፣ ባህልና ወግ ይሸረሽራል። አንዱ ዋናው መንገድ የምዕራቡን ዓለም የጾታ ርእዮተ ዓለም በሚዲያ፣ በማኅበራዊና በፓለቲካዊ ፓሊስዎች ውስጥ ማስረጽ ነው። (አንቀጽ፤ 2፣ ቍ. 5)።
ምክር - ከብዙ ትሕትና ጋር
ዓለማት ሳይፈጠሩ፤ መላለሙም ሳይዘረጋ፤ የምድርም መሠረቶች ሳይጸኑ፣ ቀላያትም በፈሳሾች ሳይሞሉ፣ የየብስም ፊት ሳይገለጥ፤ ነፋሳትም ከመዛግብት ወጥተው ሳይነፍሱ፤ ደመናት ሳያስገመግሙ፣ የብራቅ ድንፋታም ሳይሰማ፤ የዝናብ ጠብታም መሬትን ሳያርስ፣ አእዋፋት በሰማይ ሳይከንፉ፤ እጽዋታም ምድርን ሳያስጌጡ በፊት፦ ከኹሉ አስቀድሞ፦ ከጥንተ ዘላለም ስሉስ አሃድ አምላክ ስለምን መረጠን? በክርስቶስ እንኾንስ ዘንድ ስለምን ወሰነ? በፊቱ ቅዱሳን ኾነን ደግሞም ያለ ነውር ምንታይ እንኾን ዘንድ ኹሉን እንደ ፈቃዱ ምክር የሚሰራ አምላክ ስለምን ደነገገ? ብለን ብንጠይቅ ሐዋሪያ ሊኾን የተጠራው ጳውሎስ ሳያወላዳ የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ነው ይለናል። (ኤፌ 1:6) በምህረቱ ባለ ጠጋ የኾነ አምላክ በውድ ልጁ በኩል የገለጠው የጸጋው ክብር በትውልዶች መኻል ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። ቅዱሳት መጽሕፍት ድነታችን ሳይቀር በማዳኑ ብርቱ ለኾነ አምላካችን ምስጋና ያመጣ ዘንድ የተወጠነ ደግሞም የተፈጸመ መኾኑን በግልጽ ያስተምራሉ። አሁንም ሳንሰናከል ሊጠብቀን ለሚችል፣ በክብሩም ፊት ያለ ነውር ሊያቆመን ለሚችል፣ ብቻውን አምላካችንና መድሃኒታችን ለኾነ ህያው አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብርና ግርማ ሀይልና ስልጣን ይኹንለት! (ይሁዳ 22)
አምላካችን በምስጋና የተፈራ፣ ሞገስንም የጠገብ ልኡል ነው። ስሙ የተመሰገን በዘመናትም መኻል የጸና ብርቱ ነው። የፈጠራቸው የእጁ ስራዎች ያመሰግኑታል። ሰማያትም ክብሩን ያውጁለታል። ቅዱሳት መላእክቱ ያመሰግኑታል። የተቤዣቸው ህዝቡም ለስሙ ምስጋና ያቀርባሉ። ሊመሰገን የተገባው ህያው አምላክ ነውና ግኡዛንና ህያዋን በምስጋና ቃል ይባርኩታል።
ምስጋና ቀላል ሚኾንባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። የድል ማግስት የስኬትንም ማማ የተቆናጠጥን ሰሞን ምስጋና ቀላል ነው። ውጥናችን ሲሰምር ትልማችንም እውን ሲኾን አንደበታችን በምስጋና ቃል ይሞላል። ሰብል ሲሰምር፣ ጋጣውም በበጎች ሲታጨቅ፣ የሂሳብ ደብተራችን ሲደልብ፣ በወዳጆችም ስንከበብ ለማመስገን ምክንያት አለን። ባጭሩ በብሩህ ሰማይ ምስጋና አያታግልም። ጭጋጉ የበረታ ሰሞን ውሽንፍሩም ሲያይል ያኔ አቅማችን ይፈተናል። ያጀበ ሲበተን፣ ጤናም ሲቃወስ፣ ያከማቸነውም ሲነቅዝ ያኔ ምስጋና ዳገት ይሆናል። የህይወት እንግልት ፋታ አልሰጥ እያለን ምስጋና ከድንኳናችን ይሰማ ይኾን? አላውቅም!
ኢብሳ ቡርቃ
አቤቱ ሁሉን ቻይ የሆንህ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ አገራችን በጽኑ ታማለች፤ ፈውስህ ፍጥኖ ያግኛት። ምሕረትህ አያልቅምና ስማን፤ እንደ ርኅራኄም ብዛት መከራችንና ሰቆቃችንን ተመልከት፤ ካለንበትም ጨለማ አውጣን።
ከከንቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ያጨድነው መከራና ሰቆቃ ብቻ ነው። ከታሪክ አልማር ብለናል፤ ያንኑ የዐመፅና የጭከና መንገድ በመምረጥ ምዳራችንን አኬልዳማ አድርገናታል። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምሕረትህ ብዛት መልሰን። ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ የሆንኸው የመጽናናት አምላክ ሆይ፤ ሐዘን የጐዳችውን ሁሉ አጽናና፤ የልባቸውን እንባም አብስ። ለወላጅ አልባዎችና ለተፈናቀሉት እረኛ ሁን፤ ንብረታቸው የወደመባቸውን፤ በአሰቃቂ መንገድ በመደፈራቸው በአካልና በሥነ ልቡና ስብራት የተጎዱትን ፈውስ። በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ራብ ሳቢያ በሞት ጥላ ውስጥ ያሉትን ንጹሐንን በተለይም አረጋውያንን፣ ሕሙማንንና ሕጻናትን በርኅራኄህ ተመልከት። አቤቱ ልዑል ሆይ፤ በየትኛውም ጐራ ካሉ ክፉዎች ታደገን።
ጻድቅ ፈራጅና ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕያው ቃልህ፣ “ጻድቃን ሥልጣን ሲይዙ ሕዝብ ሐሤት ያደርጋል፤ ክፉዎች ሲገዙ ግን ሕዝብ ያቃስታል።” ይላል። ( ምሳሌ 29 : 2)። ይህ እውነት ነው። ለመሪዎቻችን ልቦና ስጥ። ግፍ ሲያይል፣ ፍትሕ ሲጣስና ዐመፅ በንጹሐን ላይ ካራውን ሲያሳርፍ እያዩ ዝምታን ከመረጡ የሃይማኖትና የሕዝብ መሪዎች እጅም አስጥለን። ብርቱ አዳኝ የሆንህ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጦርነትን ሻር፣ መውጫውም ከጠፋብን የዐመፅ ዑደት ታደገን። ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለብዙ ምሕረትህ ስትል የሰላምን ዝናብም ላክልን።
እንደ ክርስቶስ ማኅብረ ሰብ፣ ለአንተ የተለየ ቅዱስ ሕዝብ ልንሆን ሲገባን ከክፍፍላችን፣ እንዲሁም በመካከላችን ካሉት መንፈሳዊ፣ የአመራርና የሥነ መግባር ቀውሶች የተነሣ ቅቡልነታችን ተጎድቷል። ዘር-ተኮር በሆነ ፓለቲካዊ ክፍፍል በታወከች አገር የተስፋ አማራጭ መልእክተኛ መሆን ተስኖናል። አቤቱ ይቅር በለን፤ በምሕረትህም ብዛት ወደ አንተ መልሰን።
አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
ጆንሰንን ታዝቤዋለሁ። ትዝብቴን በአጭሩ እነሆ:-
1. የተሳሳቱ ሰዎችን ስታችኋል ብሎ ማውገዝ ያለበት የተደራጀው የቤተክርስትያን አመራር ነው ብሎ እሱ ግን እከሊት ከእንትን ቤተክርስቲያን ወታለች። እከሌ ደግሞ ከስህተቱ ታርሟል እያለ ራሱ ለመመለሳቸው ዕውቅና ሰጪና የመመለሳቸው ዜና አብሳሪ ሆኗል። በአደባባይ የሳተና ያሳተ ግለሰብን በዝግ ስላወራው ብቻ ለመመለሱ ፈጣን ዕውቅና ሰጪ ሆኗል። የሳተውስ ሕዝብ በምን መልኩ ይመለስ? ስህተት አስተማሪን የሚያቅፍ እንጂ የሚያወግዝ አካል በሌለበት ሃገር በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ ማውገዙ ምኑ ነው ስህተቱ? ግለሰቦችስ ቢሆኑ የሚበዛውን ወገን መወከልና ድምጽ መሆን አይችሉምን? ስህተት የሚያስተምሩ ግለሰቦች በየመድረኮቻቸው ቀሏቸው በነጻነት ያስተማሩትን ትምህርት ስህተት መሆኑን ከተገነዘቡ በመድረኮቻቸው ላይ ስህተት መሆኑን መናገር ለምን አቃታቸው? በግልጽ ያሳቱትንስ ሕዝብ አክብረው "አሳስቻችሁ ነበር አሁን ግን ትምህርቱ ስህተት መሆኑን ተረድቼ ትቼዋለሁ" ብለው ለመመለስ ቸኮሉ? እንደ ጆንሰን መለኪያ ከሆነ ብዙም የሳተ የለም። ሳቱ የተባሉትም ለመመለስ ቅርብ ናቸው። ታዲያ በስህተት ምክንያት የተፈጠሩትን ጉዳቶችና ምስቅልቅሎሽ በምን ለክቷቸው ይሆን?! ለአስተማሪው ወግኖ የሳተውን ሕዝብ ጉዳት ያቀለለው በምን ሚዛን ይሆን?
እየተመለከትን ያለነው እውነተኛ መመለስን ወይም ለመመለስ ቅርብነታቸውን ሳይሆን ውሸታሞች አታላዮችና አስመሳዮች መሆናቸውን ነው። ስህተቱን የተናዘዘና ያሳተውን ሕዝብ ይቅርታ የጠየቀ እኔ አላየሁም። ይልቁኑ ሲዋሹ ሲያታልሉ ስህተትን በስህተት ሲያርሙ ተመልክቻለሁ። ለአቅመ አሳችነት ያልበቁ ሰዎች ያጠፉት ጥፋት ከመለኪያም የሚያልፍ መሆኑን ስናስብ የሚያስተው ላይ በእውነት ቃል ለመጨከን እንደፍራለን። ከዚህ ውጪ ግን እጅግ አደገኛ ውስብስብ አጋንንታዊና ጥልቀት ያለውን የስህተት ነገር እያቀለልነው በሚዛናዊነት ሰበብ ጉዳቱን እንጨምረዋለን።
2. በሃገራችን ውስጥ ያሉት ለመመለስ ቅርብ የሆኑ ብዙ በመሳት ያልዘለቁ ናቸው። ስለዚህ እንደ ውጪዎቹ መታየት የለባቸውም። ስለዚህ መለኪያችን መስተካከል አለበት የሚል አሳብ ሰንዝሯል። በሙሉ ወንጌል ውስጥ ስህተት ሲኖር የማንናገር ያንኑ ስህተት ደግሞ ሌሎች ሲናገሩት የምንጮህ መለኪያ የሌለን ሰዎች ተደርገን ለመሳል የተሞከረበትም መንገድ ተገቢ አይደለም። በየትኛውም ደረጃ ስህተት ይነገር ከስህተትነት አይነጻም። ኬነት ሐገንን በሳተበት ነገር የነቀፈ አንደበት ጃፒ ሲናገረው መናገር ካቃተው መለኪያው ልክ አይደለም። ማንም በሳተበት ይጠየቃል እንጂ ያልሳተበት ነገር ታሳቢ ተደርጎ የሳተበትን ነገር መተው ተገቢ አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን በሙሉ እንደሚያቦካ የስህተት ዘርም ሁሉን የመውረስ አደገኛ ባህርይ አለው። ይህንን ከቤተክርስትያን ታሪክ መማር ይቻላል። ዛሬ በየመድረኮቹ የሚነገሩ የስህተት ቅንጣቶች ነገ ራሱን ችሎ የሚቆም ኃይማኖት ሊሰሩ እንደሚችል ማስተዋል ተገቢ ነው። ይህንን የስህተት ትምህርት አደገኛ ባህርይ በአነቃቂ ንግግሮች ሰበብ በሃገራችን ከተጀመረውና በመንግስት ከሚደገፈው የአዲሱ ዘመን ኃይማኖት እንቅስቃሴ ለመማር እንችላለን። የብልጽግና ወንጌል ለአሜሪካን አብያተክርስትያን መድከም ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ጅማሬው ግን ለአቅመ ማሳት ያልደረሰ ትንሽ ዘር ነበር።
ስለዚህ በጊዜ ቆይታ አደገኛና አስከፊ ውጤት የሚያስከትለውን የስህተት ነገር እንዲህ አቅልሎ ማየት ተገቢ አይደለም። በዐቅበተ እምነት አገልግሎት ውስጥ እንዳለ ሰው ለስህተት ትምህርት ሊኖረን የሚገባውን ንቁነትና ጠንቃቃነት በሚዛን መጠበቅ ስም እየገደልነው እንደሆነ ተሰምቶኛል። ለአቅመ መሳትና ማሳት የደረሰ ከሌለ መጽሐፍት በመጻፍ ደረጃ መቃወም ለምን አስፈለገ? ለመመለስ ቅርብ መሆናቸውን የምናረጋግጠው ቀርበን ስላወራን? መድረክ ስለተጋራን ወይስ በእውነት ቃል መዝነን? መድረክም ከተጋራን በተጋራነው መድረክ ላይ ከግለሰቡ ጋራ ያለንን የግንኙነት ዓይነት ተናግረን አቋማችንን ግልጽ አድርገን የማንስማማባቸውን ነገር አሳውቀን እንጂ ዝም ብሎ በተከፈተ በር ሁሉ ዘለን የምንገባ አቋም የሌለን ሰዎች መሆን የለብንም። ለምናደርገው ነገር እኛው መለኪያ ከሆንንና የዐቅበተ እምነት አገልግሎት ሚዛን አድርገን ራሳችንን በየመድረኩ የምናስተዋውቅ ከሆነ የቆምነው ለእውነት ነው ወይስ ለራሳችን? የሚል ግምት ያሶስድብናል። ስለዚህ መለኪያችንን መለስ ብለን ብንፈትሽ መልካም ነው።
ቸር እንሰንብት!!!
ዛዲግ ብርሃኑ
ቻናል ጥቆማ
Channel recomendation
The is a channel created for the purpose of sharing good Christian books from the reformed Christianity world.
/channel/christiangoodbooks
ዛሬ! ቅዳሜ ከ9:00 ጀምሮ! በኡራኤል መካነ ኢየሱስ!
=====================
በነገራችን ላይ ...
ተሐድሶ ጽዩፍ ነው። ቃሉ ለቆሸሸ አላማ ሲውል፣ ድነት መሃከለኛውን ሲስት፣ ፀጋ ሲራከስ ይጸየፋል። ባህሪው ነው! ታሪክ ትውፊት ስርአት ብለው ቆሻሻ ካባ ደርበው ሲያላዝኑበት በቅዱሱ ቃል ወንፊት ያቀላቸዋል፣ ያጠላቸዋል። ቃሉ ያላሳለፈውን አያሳልፍም፣ ከቃሉ ውጪ ምንም ይሰማ ዘንድ አይወድምና።
ተሐድሶ ተመላሽ ነው.... ወደ መጀመሪያውና ወደሐዋሪያቱ ቤተክርስትያን። ወደ ጤነኛውና መጀመሪያው ይሸሻል፣ ቃሉን ተከትሎ እግሬ አውጪኝ ነው። ተሐድሶ አዲስ ስርአት፣ አዲስ ወግ፣ አዲስ ሃይማኖት ማምጣት ሰንደቁ አይደለም። ምጡ የመጀመሪያውንና የጥንቱን ክርስትና መውለድ ብቻ ነው!
ተሐድሶ አይኑም፣ ልቡም ፈቃዱም ሆነ ፍላጎቱ ያለው የተሰቀለው የሞተው ከሞትም የተነሳው ዳግም የሚመጣው ክርስቶስ ላይ ብቻ ነው። ክርስቶስና ያፈሰሰው ፀጋ ሲደበዝዝ ጉድ እንደሚፈላ ያውቀዋል፣ ከክርስቶስ ውጪ ላሳር ባይ ነው። ከክርስቶስ ውጪ ሁሉ ጨለማ፣ ሁሉ ገደል፣ ሁሉ ሃሰት ነው! ለዚህ ነው ነገረ መስቀሉ ብቻውን መሃከለኛ አስተምህሮዬ ነው ብሎ የሙጥኝ የሚለው። ክርስቶስን እንደ ሁሉ ነገር ማማከያ አድርጎ ይወስደዋል።
ተሐድሶ የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋፋ ስርአት፣ ወግ አልያም ግለሰብ ሲነሳ ተቆጪ ነው። የቱንም ያህል ጡንቸኛ ተነስቶ ለመፋነን ቢጥር ከመርሁ ፍንክች አይልም። በአስተምህሮውም ሆነ በልምምዱ ብቸኛው ክብር የተገባው እግዚአብሔር እንደሆነ ያውጃል። ክብር ለእግዚአብሔር ልበ ምቱ ነው።
አዎ አሁንም፣ በዚህ ዘመንም ቢሆን ቃሉን የሚክድን፣ ክርስቶስን የሚያደበዝዝን፣ ፀጋውን የሚያክፋፋን፣ የእግዚአብሔርን ክብር አሽቀንጥሮ የሚጥልንና እምነትን የሚበርዝን የትኛውንም ወግና ባህል ስርአትና ልምምድ እንቃወማለን!
ኑና ተሐድሶውንና ድኅረ ተሐድሶውን እንዘክራለን!
#ተሐድሶው_ሲታወስ
አማኑኤል አሰግድ
"የህይወትለውጥ" ( conversion )በ1ኛተሰሎንቄ መልዕክት በትክክል እንደተገለፀው ሐጢአተኛው በመለኮታዊ ፀጋ ከሐጢአት እና ከጨለማው ሃይል ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መመለሱን አመልካች ነው: ይህም ከንቱ እና በድን ከሆነው ተለይቶ ህያው እና ዕውነተኛ የሆነውን አምላክ ለማገልገል እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሳውን ከሚመጣውም ቁጣ አዳኝ የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን ከሰማይ ለመጠበቅ ያስችለዋል::
ይህን ለውጥ በሰው ሕይወት ማምጣት የሚችለው ደግሞ "ቃለ እግዚአብሔር" ብቻ ነው:"ሰው ሠራሹ" እና "ልዩው ወንጌል" (ወንጀልየሆነው)ትውልድንገዳይ እንጂየሚፈለገውን"የህይወትን ለውጥ" ሊያጎናፅፈው አይቻለውም: ስለዚህም የወንጌሉን ደረጃ እና ጥራት ትክክለኛነት ማጣራት የግድ ነው: ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ሃይል የሚሰበክ እንጂ "የሰው ወሬ" እና "ጩኸት" አይደለምና!
ሌላው ይህንን ክቡር የሆነ ወንጌል የሚሰብኩ ሰዎች በትክክል "ተልዕኮ" ያላቸው ሊሆኑ ይገባል: ሳይላኩ እንዴት?....እንደተባለው:: ተልእኮ ያላቸው ወንጌሉን ሳያቀጣጥኑ እና ከርሱም አትራፊ ለመሆን ሳይከጅሉ እንዲሁም ክብርን ከሰው ሳይጠብቁ አባት ለልጆቹ እንደሚያደርግ የሚመክሩ የሚያፀኑ ለተልእኮእቸው ታማኝ የሆኑ መሆናቸው ለህይወት ለውጡ አስትዋፅዖዋቸው የጎላ ነው::
በተጨማሪ ሰሚው ሲቀበልም ቃሉ "በሚያምኑት ሁሉ ላይ በዕርግጥ እንደሚሠራ" የመለኮት ቃል እንጂ የሰው አለመሆኑን እርግጠኛ መሆን ያስፈልገዋል: "የእግዚአብሔር ቃል ...የሚሠራ ነውና" የተባለው ለዚህም አይደል! ቃሉም ለመስራት ከሰው "መታዘዝን" ጠያቂ መሆኑ ሳይዘነጋ:: ይሄ "የህይወት ለውጥ" እግዚአብሔርን ወደመምሰል አሻጋሪ ነው: ሣይመስሉ "አባትነቱን" ማወጅ " ያልወለድኩት ልጅ አባባ ቢለኝ አፌን ዳባ ዳባ አለኝ" ነው የሚሆን( ዳባ ለአፍ የማይጣፍጥ: ከሣቴ ብርሃን)
በመጨረሻም "የህይወት ለውጡ" አዎንታዊ አስተሳሰብ(positive thinking )ሳይሆን በሁሉም ቦታ ለሌሎች የሚታይ የሚዳሰስም ነው:: የተሰበኩት የተቀበሉት የሚቆሙበት ደግሞም የሚድኑበት ወንጌል ሳይኖር በከንቱ( በጨበጣ) አማኝ መባል አይዘገንንም!
እና ኑና የዚህን ዓመት የተሀድሶው ሲታወስ "መሪ ሃሳብ" በጋራ እንካፈል: ለውጥ አያሻንም ትላላችሁ?
ወንጌላዊ ደሉ ጸጋዬ
ክርስትና የመለወጥ እምነት ነው። ቀደም ብሎ ከነበረ እምነት ወደ አዲስ እምነት። ድሮ ከነበረ እውቀት ወደ አዲስ እውቀት። ከቀደመ የረከሰ ሕይወት ዘዬ ወደ ቅዱስ የሕይወት መንገድ። መለወጥ አልያም ዞር ማለት ነው። ብዙ ታሪኮች የሚነግሩን እውነታ ክርስትና የመለወጥ እምነት መሆኑን ነው። ክርስትናን ያለ መለወጥ ማሰብ የማይቻል መሆኑን ቅዱሳት መጽሐፍት ያስረግጣሉ።
የብሉይ ኪዳን ምንባባት መለወጥን ብዙ ጊዜ የሚያያይዙት በንስሃ በእግዚአብሔር ፊት ከመሆን ነው። መለወጥ ከሃጢአት ዞር በማለት ወደ ህያው አምላክ በእምነት መቅረብ እንደሆነ ይተርካሉ (1 ነገሥት 8:48 ፤ ኢሳያስ 6:10 ይመልከቱ)። ለዚህም ነው ኪዳኑን ሳያከብሩ ፍርድ እየተነገራቸው እንኳን በንስኅ ከተመለሱ እግዚአብሔር እንደሚሰማቸው ቃል የተገባላቸው (1 ነገሥት 8:48)።
መለወጥ በአዲስ ኪዳን የክርስቶስ አማኝነትን ለመጠቆምና ወደ መሲሑ መመለስን ለማሳየት አገልግሎት ላይ ውሏል (1ጢሞ 3:6፤ ሮሜ 16:5)።
ወንጌላውያን አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት አድርጎ የሚናገረውን መለወጥ/conversion በልዮ ሁኔታ ይመለከቱታል። በዳግም ልደት በኩል የሚገኘው ይህ የሕይወት ለውጥ መሠረታዊ ነው። ይህ መመለስ በንስኅ ወደ እግዚአብሔር ልጅ መንግሥት ይጠይቃል። እግዚአብሔር በልጁ በኩል ወዳወጀው ብሎም ወደመሠረተው መንግሥት ለመግባት ንስኅ መግባት ቀዳሚ ነው።
ንስኅው ግን ያለ ንስኅ ፍሬ ከንቱ ነው። መመለስ በንስኅ ቢጀምርም በንስኅ ፍሬ መታጀብ አለበት። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ «[...]ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ።» (ሐዋ. ሥራ 26:20) በማለት ንስኅ መግባትን ከሕይወት ለውጥ ጋር የሚያዛምደው።
ለዚህ ነው ክርስትና የመለወጥ እምነት ነው የምንለው። በዘመናችን ያለው ወንጌላዊ አማኝ እንደልቡ ሲሆን፣ ከርቱዕ ትምህርት ሲፋታ፣ ለልምምዱ ለከት ሲያጣ፣ ቅይጣዊነት ሲገዝፍ፣ የሕይወት ጥራት ሲጎድልና በስመ ክርስትና ክርስትና ሲሰደብ ተጠየቅ ውስጥ የምናስገባው መለወጡን መሆን አለበት። ስለዚህም በእውነት ክርስቲያናዊ ለውጥ ላይ ደፈር ብለን መነጋገር ያለብን ይመስለኛል።
.
ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር የፊታችን ቅዳሜ ከሰዓት ብትመጡ ወንድም Tegegn Mulugeta ደግሞ ምርጥ አድርጎ በእለቱ ከቃለ እግዚአብሔር በርእሰ ጉዳዮ ላይ ያስተምረናል።
አማኑኤል አሰግድ
እነሆ ቆሜያለሁ! - HERE I STAND!
ሉተር በዊተንበርግ ዮኒቨርስቲ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ 95 አናቅፅቱን ካስቀመጠ በኋላ የተለያዩ ውግዘቶችና ስደቶች ደርሶበታል። ባነሳቸው የተሐድሶ ሃሳቦች የአደባባይ ሙግት እንዲያደርግ በጳጳሱ ወዳጅ ዶ/ር ጆኸን ኤክ ገፋፊነት በሌፕዢግ ከተማ(1519) ክርክር ተደርጎ ነበር። ሁለቱም ወገኖች ሙግቱን ባያሸንፉም፣ ዶ/ር ጆኸን ማርቲን ሉተር ቤተክርስቲያኒቱና ጳጳሱ መሳሳታቸውን እንደሚቀበል እንዲናገር አድርጎት ነበር። ይህ ደግሞ ጳጳሱና የቤተክርስቲያን "ካውንስል" የማይሳሳቱ መሆናቸውን መካድ ጭምር ነበር። ቤተክርስቲያን ተሳስታለች ማለት በሞት የሚያስቀጣ ክስ ነው። በተመሳሳይ ውንጀላ ጆን ሁስ ከመቶ አመታት በፊት በእሳት አቃጥለው እንደገደሉት ልብ ይሏል።
ዶ/ር ኤክ ወደ ሮም በመሄድ ሉተርን excommunicate የሚያስደርግ ደብዳቤ እንዳሰበው በፍጥነት ባይሆንም በጳጳሱ ማሕተም የተፃፈ ይዞ መጣ። ደብዳቤው ሲጀምር " Arise, O Lord, and judge thine own cause.... A wild boar invaded thy vinyard." ይል ነበር። ሉተርም ደብዳቤው በደረሰው ስድሳ ቀናት እንዲያስተባብል ጥሪ ቢቀርብለትም ሳይቀበለው ቀረ።
ልዑል ፍሬድሪክ (አስተዋዩ) የሚወደውን መነኩሴና ፕሮፌሰር አሳልፎ ለመስጠት አልወደደም። አብዛኛው የጀርመን ህዝብም ከጳጳሱ ይልቅ ከሉተር ጋር ወገንተኝነታቸውን አሳዮ። በዚህም ምክንያት ሉተር ከሚኖርበት አካባቢ ውጪ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ጳጳሱ የፃፉለትን ደብዳቤና ሌሎች የካቶሊክ ህግጋት(ቀኖና) መጽሐፍትን ህዝብ በተሰበሰበበት በማቃጠልና የሚያምንበትን እምነት አስረጂ ጽሁፎችን መበተን ጀመረ። ምስጋና ለማተሚያ ማሽን ይግባና የምካቴ ጽሁፎቹ በፍጥነት ጀርመናዊያን እጅ ለመግባት በመቻላቸው ማህበረሰቡ እያንዳንዱን ጽሁፎቹን ሸሽጎ ለማኖር አልቸገረውም።
HERE I STAND!
የቤተክርስቲያን ጉዳይ የነበረው ቀስ በቀስ ፖለቲካዊ ይዘት መያዝ ጀመረ፣ ልዑል ፍሬድሪክ የጳጳሱን ቀጥተኛ ትእዛዝ አለመቀበሉን ልብ ይሏል። ጳጳሱ የስፔን ንጉስ የሆነውንና በወቅቱ የጀርመንም ንጉስ የሆነውን ቻርልስ አራተኛን የሆነ እርምጃ እንዲወስድ ግድ አሉት። ንጉሱም ከፈረንሳይ ንጉስ ጋር ላለበት ጦርነት የጳጳሱን ድጋፋ ይሻ ስለነበር ለመስማማት አላንገራገረም። በዚህ ላይ ደግሞ አክራሪ ካቶሊክና የቤተክርስቲያን መተቸት የማያስደስተው ነበር። በተቃራኒው ደግሞ ንጉሰ ነገስት እንዲሆን የመረጡትን የጀርመን ልዑላንን ማስከፋት አልፈለገም። አንዱ ልዑል ደግሞ የሉተር ወዳጅና ጠባቂ ጭምር ነበር።
ንጉስ ቻርልስ አራተኛ ሉተር በዎርምስ በምትገኘው ዲየት (1521) ላይ ለሁሉም ልዑላንና የጀርመን የነፃ ከተሞች መሪዎች ጉባኤ ላይ እንዲገኝና ጉዳዩን እንዲያስረዳ ይጋብዘዋል። ሉተርም ያለመያዝ መብት በማግኘቱ፣ ቢከሰስም እንኳ ወደ ግዛቱ በሰላም እንደሚመለስ ቃል ስለተገባለት ዎርምስ ለመገኘት ሄደ። በወዳጆቹ «ጆን ሁስንም ተመሳሳይ ብለው ነው አቃጥለው የገደሉት» ተብሎ ቢመከርም ዎርምስ ከመገኘት አላገደውም።
በዎርምሱ ጉባዔ ሉተር የጻፋቸውን መጽሐፍት በጠረጴዛ አስቀምጠው አሳይተውት ያለውን ነገር እንዲክድ ጠየቁት። ደግሞስ ከቀደምት ስነመለኮታውያን በላይ አስባለሁ ብለህ የምትለው ማን ስለሆንክ ነው ብለው አበሻቀጡት።
ነገር ግን ማርቲን ሉተር እስከ ዎርምሱ ስብሰባ ቀን ድረስ የተናገረውን አልክድም ለማለት ይህንን ተናገረ፦
"I cannot and will not recant anything, for to act against conscience is neither safe for us, nor open to us. Here I stand, I can do no other. God help me. Amen."
ሲተረጎም፦ «ስቻለሁ የምለው አንዳች ነገር የለኝም፤ ኅሊናዬ ከሚያዘኝ ውጪ መሆን ትክክልም ሆነ አግባብ አይደለም። እነሆ፤ እዚሁ ቆሜያለሁ፤ ከዚህ ውጪ ምንም ላደርግም አይቻለኝም። እግዚአብሔር ሆይ እርዳኝ። አሜን።»
የመዳን መንገድ ክርስቶስ ብቻ፣ እንዲያው በፀጋ ብቻ፣ በእምነት ብቻ የሚገኝ ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የሚሆን፤ የቤተክርስቲያንም ሆነ የቅዱሳን የበላይ ቅዱስ ቃሉ ብቻ የሚለው ሃሳቡን ለማጠፋ/ለመለወጥ ፋቃደኛ ባለመሆኑ ንጉስ ፈረደበት። ንጉሱ ቃል የገባውን በማክበር ወደ ቤቱ በሰላም እንዲመለስ ቢያደርገውም የትኛውም ህግ ለሉተር ከለላ እንደማይሰጠው ወስኖበት ነበር።
መውጫ
ተሐድሶ ብቻ መቆምን ይጠይቃል። ዘመንን መረዳትን፣ መጽሐፍትን መመርመርን፣ ለእግዚአብሔርና ለህሊናችን ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። ተሐድሶ ወደ አባቶችና አያቶች ለመንፀሪያ መመልከትን አንደ ቄንጥ አያይም። የድነትን መኸከለኛ፣ የእምነትን ፈፃሚ፣ የእግዚአብሔርን መገለጥ፣ ትምሕርተ ክርስቶስን አደብዛዥን ሁሉ ለመቃወም ሁለቴ አያስብም። ተሐድሶ ቃለ–እግዚአብሔር ማሕደረ–ክርስቶስ በተባለችው ቤተክርስቲያን ሲደፈጠጥ ጥሪውን በማማ ላይ ያሰማል፤ እነሆኝ ለህሊናዬም ለቃሉም ቆሜያለሁ ይላል። እግዚአብሔር ልጁን በገለጠበት ቃል በኩል ለኅሊናዬ ብቻዬን እንኳን ቢሆን እቆማለሁ የሚል እውነትና ፅናት ያድለን።
ቅዱሳት መጽሐፍት ለሚሉት ብቻ መገዛት ለእግዚአብሔር መገዛት ነው!
#HERE_I_STAND
#እነሆ_ቆሜያለሁ
#ተሐድሶው_ሲታወስ
አማኑኤል አሰግድ
“ስሜ ከጠፋው በላይ፣ ሰዎች ሊናገሩ የሚችሉት የከፋ ነገር የለም። ከራስ እስከ እግር ጥፍሬ ድረስ፣ ተወግጃለሁ፤ እስከ ጥግ ድረስ ያልሆኑትን ምስል ተሰጥቶኛል። መልካምነቴን በተመለከት፣ አሁን መልከ ጥፉ ከተደረገበት ባላይ፣ የከፋ ማደረግ ማንም አይችልም። መጥፋት የሚችለውን ያኽል ጠፍቶአልና። ያልተጐዳ ምንም የቀረኝ ማንነት የለም።” (An All-Around Ministry Addresses to Ministers and Students, 1872, 159)
በእነዚህ ነውጦች ሁሉ መካከል፣ “የነፍስ ድቅድቅ የጨለማ ምሽት” በማለት በሚጠራውና አልፎ አልፎ በሚነሣ ሰበብ የለሽ ድባቴም ይቸገር ነበር። በአንድ ስብከቱ መካከል፣ የደባቴውን ክብደት እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “ባለፈው ሳምንት በሶፋ ላይ ገደም ባልሁበት፣ ድባቴ ድንገት መጣና ልቤን አወረደው። ለሰዓታት እንደ ሕፃን ልጅ አለቀስሁ፤ ምክንያቱን ግን አልውቀውም ነበር።” (The Christian’s Heaviness and Rejoicing: 1 Peter 1:6, November 7, 1858)። ጋውት (Gout) የተሰኘው የጣቶችና (በተለይም የእግር አውራ ጣት) የመገጣጠሚያዎች ቁርጥማት (አርትራይተስ) እና የኩላሊት ሕመም፣ መከራውን ቀላል አላደረጉለትም። የጋውት ድንገተኛ ጥቃት ሲመጣ የሚሰማው ስለታም የሕመም ስሜት፣ አውራ ጣትን በመዶሻ የማድቀቅ ያኽል ነው።
ከማሕፀን ሕምም ጋር በተየያዘ ምክንያተ በተካሄደ ያለተሳካ ቀዶ ጥገና፣ ለ 27 ዓመታት ከወገብዋ በታች ሽባ የነበረችውን ባለቤቱን ሱዛናናን ያስታምም ነበር። የመጨረሻዎቹ ጥቂት ዓመታቶቹ፣ የደስታ አልነበሩም። ልቡ ወድቆ ነበር። ቀድሞ በሞት የተለያት ባለቤቱ፣ “ለእምነቱ የነበረው ተጋድሎ፣ ሕይወቱን አስከፍሎታል” በማለት መስክራለታለች።
ነብዩ ኤልያስ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” በማለት የጸለየበት ምክንያት ይኽው የልብ መውደቅ ነበር።
በብዙ መከራ ውስጥ፣ በትችት፣ በመገፋት ወይም ርኅራኄ በሌላቸውና በሥጋውያን አስቸጋሪ መሪዎች ጫና ሥር የሚያገለግሉ ብዙ የጌታ ባሪያዎች አሉ። አብዛኛዎቹን ሚዲያው አያውቃቸውም። በዚያ ላይ ቤት ኪራይ በመክፈልና ልጅን በማሳከም፤ አስቤዛ በማድረግና ለልጆች ትምህርት ቤት በመክፈል፤ መድሃኒት ለራሳችው በመግዛትና የባለቤታቸው ጥርስ በማሳከምና በመሳሰሉ አስከፊ የኑሮ ምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ እያለፉ፣ በየሰንበቱ በታማኝት የሚያገለገሉ ባሪያዎች አሉ። በአንድ በሌላም መንገድ፣ በአገልግሎት ጉዞ ውስጥ፣ “ዮሴፍን የሚሸጡ ወንድሞች፣ ዳዊትን የሚያሳደዱ ሳዖሎች፣ በሙሴ ላይ የሚነሱ ማሪያሞችና አሮኖች፣ ክርስቶስን አሳልፈው እንደሰጡት ያሉ ደቀመዛሙርት፣ ጴጥሮሶችና ይሁዳዎች፣ ዴማሶች፣ አንጥረኞቹ እስክንድሮሶች፣ ሌሎቹ” አይጥፉም። በአገልግሎት ውጣ ውረድ ውስድ፣ ቅዱስ ቃሉ ሁሉ የጠራችሁ እርሱ የታመነ ነው እንደሚል፣ እግዚአብሔር ታማኝና ሉዓላዊ ነው።
እጅግ በከበደ መልኩ ሐዋርያት በመከራ ስለ ታጀበው የወንጌል አገልግሎታቸው ብዙ ጊዜ በምስጋና ልብ ተናገረዋል። በዚህ ዐውድ ሁለቱን መጥቀስ አግባብነት አለው፡፤
"ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም፤ ብንሰደድም ተጥለን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም። የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችን እንዲገለጥ፣ እኛ ሕያዋን የሆንን ሁል ጊዜ ስለ ኢየሱስ ለሞት ዐልፈን እንሰጣለንና። እንግዲህ ሞት በእኛ ይሠራል፤ ሕይወት ግን በእናንተ።" (2 ቆሮንቶስ 4:8-12)
“ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ . . . ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሁሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ።” (1 ጴጥሮስ 4:12-19)
አገልግሎት “ሙያ” ያልሆነበት ቀዳማዊ ምክንያት ከልብ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ነው። በፍትሕ የለሽ በደልና ስብራት የቈሰለ ልብን ተሸክሞ፣ በታማኝነትና በመሰጠት ማገልገል ትልቅ ጽናትና ጸጋ ይጠይቃል። ስፐርጀን እንዳለው፣ “አገልግሎታችን ከአእምሮ ሥራ በላይ ነው። የልብ ጉዳይ ነው፤ የነፍስ ውስጠኛ ትጋት። (Spurgeon, Lectures to My Students, [Zondervan Publishing House, 1972], 156)
በተሰበረ ልብ እንዴት በሙሉ ኀይልና መሰጠት ለቅዱስ ቃሉ ታማኝ በመሆን ማገልገል ይቻላል? ስፐርጀን እንዳለው “ለራስ በመሞት በእግዚአብሔር ሉዓላዊነትና ጸጋ በመደገፍ ብቻ ነው። በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የነበረው ጽኑ እምነት፣ በልቡ የፈሰሰው ወሰን የለሽና ሁሉን አስጣይ የክርስቶስ ፍቅር፣ በጌታ ጸጋ ተደጋፊነት፣ የጸሎት ትጋቱን፣ ብቻውን ቢቀርም እንኳን ለወንጌል ንጽሕና የነበረው ቀናዒነት፣ ዐቅሙ ነበሩ።
“በብዙ [መከራ] በጌታ አገልግሎት ብንዝልና ያለ ዕድሜያችን ብንሞት፣ ክብር ለግዚአብሔር ይሁን። ምድር ትንሽ፣ ሰማይ ደግሞ ብዙ ይኖረናል ማለት ነው።” (An All Round Ministry, 126–127).
ባለቤቱ ሱዛና እንደ መሰከረችለት፦
"አንዳንድ ጊዜ, ለዓመታት የጌታ ቃል ሲያጠና፣ ሲያስብና ሲጽልይ የነበረበት የጥናት ክፍሉ እገባና በወንበሩ ሥር እንበረከካለሁ። የእጅ መደገፊያው ላይ ራሴን አሳርፍና የልቤን ጥልቅ ሐዘን በእንባ አያፈሰስሁ ብቸኝነቴን ለጌታ አጫውተዋለሁ። የእግዚአብሔርን ክብር ያስተናገደው ያው ክፍል አሁንም በዚያው ክብርና ቅድስና እንደተሞላ ውስጤን ይሰማዋል። በርግጥ ባሌ ሁሉን በመልካም የጨረሰ ታማኝ ባሪይ ነበር።”
ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
ሰሞኑን ለግሌ እያጠናሁ ካለሁት ከዮሐንስ ራዕይ ብዙ ትምህርት እየተማርኩ አለሁ፡፡ አንዱን በአጭሩ ላካፍላችሁ . . .
የኤፌሶን ቤ/ክ ብርቱ የሆነችበት ነገር አላት፡፡ ይህም የምትሰማውን ነገር የመመርመር አቅሟ ነው፡፡ ጌታ እንዲህ ነበር ያላት፦ “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ፦ ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ ታግሠህማል፥ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም” (ራዕ 2፡2-3)፡፡
በኤፌሶን ቤ/ክ ውስጥ ሐዋሪያት ሳይሆኑ “ሐዋሪያት ነን” የሚሉ እንደነበሩ ከዚህ ክፍል ልንረዳ እንችላለን፡፡ “ሐዋሪያት ነን” ስለሚሉም ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር፡፡ ይሁንና ትምህርታቸው ስህተት ነበረበት፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱም የእነዚህን ሰዎች ትምህርት መመርመር ጀመረች፡፡ እናም ትምህርታቸው ስህተት ሆኖ ተገኘ! ስህተት ሆኖ ያገኘችውንም በጽናት ትቃወም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ” በማለት የተናገራት፡፡
የኤፌሶን ቤ/ክ የምትሰማውን ትምህርት በመመርመር ብርቱ ብትሆንም እንኳን በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም አልነበረችም፡፡ ችግሯ ደግሞ ፍቅርን የሚመለከት ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው የነበራት ፍቅር አሁን ካላት ጋር ሲወዳደር ፍቅሯ ቀዝቅዟል፤ አንደድሮዋ አይደለችም፡፡ ይህ ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት አልነበረም፡፡ ስለዚህም ይነቅፋታል፦ “ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና” (ራዕ 2፡4) በማለት፡፡
በስመ ሐዋሪያነት የተሰየመ (ራሱን የሚጠራ) ሁሉ “ትክክል ነው” ማለት አይደለም! ትክክለኛ ማንነቱ ስሙ ላይ ሳይሆን ትምህርቱ፣ ደግሞም ግብሩ ላይ ነው፡፡ በዘመናችንም አንዳንድ ሰዎች “በሐዋሪያነት”፣ “በነቢይነት”፣ “በፓስተርነት”፣ “በአገልጋይነት” እና በሌሎችም መንፈሳዊ በሚመስል የአገልግሎት መጠሪያ ስለተጠሩ ብቻ በተለያዩ መንገዶች የሚያስተላልፏቸውን ትምህርቶቻቸውንና ስብከቶቻቸውን ዝም ብሎ በየዋህነት መስማትና መቀበል ተገቢ አይደለም፡፡ ከመቀበላችን በፊት የምንሰማውን ትምህርት መመርመር አስፈላጊ ነው!! ጥቅስ የጠቀሰ ሁሉ ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም የምንሰማውን ትምህርት ወይም ስብከት መመርመር ተገቢ ነው! ከኤፌሶን ቤ/ክ እንማር፡፡ የምንሰማውን ነገር መመርመር መልካምና የሚበረታታ ነገር ነው! ይህን እያደረግን ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄድ ሕይወትም አለ - የፍቅር ሕይወት፡፡ እግዚአብሔርንም፣ ሰዎችንም መውደድ፡፡
መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት ጥሩ ነው፡፡ ስነ መለኮታዊ ትንታኔ መስጠትም ተገቢ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥንካሬ የምንሰማውን እንግዳ ትምህርት ለመመርመርና ብስሉን ከጥሬ ለመለየት ይረዳናል፡፡ ታድያ ይህን በምናደርግበት ጊዜ ፍቅርን በመጣል መሆን የለበትም፡፡ “እውነትን በፍቅር” (ኤፌ 4፡15) ልንይዝ ያስፈልገናል፡፡ እውነትን በፍቅር የመያዝን አስፈላጊነት አስቀድሞ በሐዋሪያው ጳውሎስ በኩል ለኤፌሶን ቤ/ክ መነገሩ የእግዚአብሔር መንፈስ ምን ያህል አስቀድሞ እያሳሰባት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
የዘመናችን ቤ/ክ “ፍቅር፣ ፍቅር” እያለች መክነፍ የለባትም፡፡ “ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና” (ራዕ 2፡6) ተብሎ ለኤፌሶን ቤ/ክ እንደተጻፈላት የተመረመረ ፍቅርን ልትይዝ ያስፈልጋታል! መመርመር የተሳናት ቤ/ክ በ"ፍቅር" ስም እውነቷን የሸጠች ናት፡፡"ኒቆላውያንን" ታቅፋለች! ምልልሷም ሽንገላ ይሆናል፡፡ እውነትንም፣ ፍቅርንም ብትይዝ ግን ሚዛናዊነትን የተላበሰ ሕይወት ይኖራታል፡፡
ሚዛናዊነትን ባልተላበሰ ሕይወት እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም፡፡ የፍቅር ሕይወት ኖሮን በቃሉ ካልታጠቅን የመጣው ነፋስ ሁሉ ይወስደናል፡፡ ያን ጊዜ “የምነቅፍብህ ነገር አለኝ” ተብሎ እንደተጻፈው በእኛም እንዲሁ ይሆንብናል፡፡ በእውቀት የታጠቅን ሆነን ፍቅር ከሌለን ወደ ትዕቢት ይመራናል፡፡ ስለዚህም ሁለቱንም መያዝ ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ እንዲህ ባለ መልኩ ሚዛናዊ ሕይወት የመምራትን ጥበብ እግዚአብሔር ያብዛልን!
ልደቱ አለሙ (ዶ/ር)
"የጨለማው ዘመን" በደጅ ነው!
የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚጠናበት አንዱ ምክንያት በአንድ ወቅት በታሪክ የተፈጠረውን ስህተት ላለመድገም ነው። ነገር ግን ጀርመናዊው ፈላስፋ ጆርጅ ሄጋል (Georg Hegel) "ከታሪክ የተማርነው ከታሪክ ምንም መማር እንደማንችል ነው" ብሎ እንደተናገረው ዛሬም ወንጌላዊቷ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከታሪክ የተማረች አትመስልም።
ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ቤተክርስቲያን በታሪኳ "የጨለማ" የሚባል ዘመን ውስጥ ገብታ ታውቃለች። ወደ "ጨለማው ዘመን" ከመግባቷ በፊት ግን ከውልደቷ ዘመን ጀምሮ በተከሰቱ የተለያየ መልክ ባላቸው የስህተት ትምህርቶች እና ልምምዶች በብዙ ስትናጥ ኖራለች። የጥንት አባቶችም ለወንጌል የጨከኑ ስለነበሩ የወንጌሏን ንፅህና ጠብቃ እስከ 4ኛው ክ/ዘመን መባቻ ድረስ ለመቆየት ቻለች እንጂ።
ነገር ግን የሚያሳዝነው ከ5ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ሉተር "ተሃድሶ!" ብሎ እስከተነሳበት እስከ 16ኛው ክ/ዘመን ድረስ ቤተክርስቲያን ለአንድ ሺህ ዓመታት "በጨለማ" ውስጥ ኖራለች። ይህ የጨላማ ዘመን የስህተት ትምህርት እና የስህተት ልምምድ በቤተክርስቲያን ውስጥ የተስፋፋበት፣ መሪዎች ራሳቸውን በክርስቶስ ቦታ አስቀምጠው በህዝቡ ላይ የሰለጠኑበት፣ ቤተክርስቲያን ከመንግስት ጋር ግልፅ ጋብቻ የፈፀመችበት፣ ጦር ሰብቃ እና "የመስቀል ጦርነት" አውጃ ነገስታቱን ከፊት አሰልፋ ሃይማኖቷን በሰይፍ ለማስፋፋት የተነሳችበትጊዜ ነበር። ጨለማ ውስጥ የነበረችበት ጊዜ ነበር።
ታዲያ ቤተክርስቲያን በዚያ "በጨለማው" ዘመኗ በቢሊዮን የሚቆጠር አባላት ሰብስባለች፣ ትልልቅ እና ለዐይን ማራኪ የሆኑ ህንፃዎችን (ካቴድራሎችን) ገንብታለች፣ ስረዓቶቿንም ፈፅሞ አላቋረጠችም። የቋረጠው ንፁህ የሆነውን የክርስቶስ "ወንጌል" መስበኳ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ዋና ነገሯ በምድር የምትኖርበት ምክንያቷ ነበር። ቤተክርስቲያን ግን እንኳን ንፁህ የሆነውን ወንጌል ልትሰበክ መፅሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የሚተጉትን ማሳደዱን ስራዬ ብላ ተያይዛው ነበር። ጨለማ ውስጥ ገብታለቻ! ለዚህ "ጆን ዊክሊፍ" እና "ጆን ሁስ" ላይ የፈፀመችው ግፍ ጥሩ ማሳያ ነው። "ተሳዳጇ" በተራዋ "አሳዳጅ" ሆና ነበርና። በጨለማ ዘመን ታሪኳ።
ወገኖች ዛሬም ወንጌላዊቷ የኢትዮጵያ ቤተክርሰቲያን ለንፁሁ የወንጌል ትምህርት ጀባዋን ከሰጠች፣ የስህተት ትምህርት እና የሃሰት ልምምድ ጠርንፎ ከያዛት፣ መሪዎቿ ከተኩላ ከተዛመዱ፣ ከመንግስት (ከቤተመንግስት) ጋር ስውር ፍቅር ከጀመረች፣ በሃሰትና በእውነት መካከል የነበረው ግልፅ መስመር ጠፍቶባት "ቅይጣዊነት" መገለጫዋ ከሆነ፣ ሰው መስራቷን ቸል ብላ ያላትን ሃይል ሁሉ ለህንፃ ግንባታ መጠቀም ከጀመረች "የጨለማው ዘመን" ነው ማለት ነው። ከታሪክ ከተማርን የምንማረው ይህንን ነው። ተሃድሶ! ተሃድሶ! ተሃድሶ! ያስፈልገናል።
ቴዎድሮስ ተጫን
የሃሳዊያኑ ፍኖተ ካርታ
አንድ አስተሳሰብ (ሰናይ ቢሆን እኩይ) በማህበረሰብ መካከል ሰርፆ ገዢ ሃሳብ ሆኖ ለመውጣት ፍኖተ ካርታ (Road Map) ያስፈልገዋል። የጠራ ግብ (መዳረሻ)፣ ስልት፣ በየደረጃው የሚጠበቅ ውጤት እና የታሰበባቸው እርምጃዎችን ያላካተተ ማንኛውም "ሃሳብ" የትም አይደርስምና። ይላሉ የመስኩ ተመራማሪዎች። በሀገራችን የሚገኙ "ሃሳዊያንም" የራሳቸው "ፍኖተ ካርታ" አላቸው። በእኔ ግምገማ የሃሳዊያኑ ፍኖተ ካርታ አራት ደረጃዎች አሉት። በአሁን ወቅት ደግሞ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ተሸጋግረዋል።
ወገኖች ስለ ሃሳዊያን ያለን ምልከታ በልካቸው መሆን አለበት። አቅልለንም አግዝፈንም ማየት አደጋ አለውና። አንዳንዶቻችን እንደምናስበውም ሃሳዊያኑ "ሞኛሞኝ" አይደሉም። ቤትና መኪና መግዛት ላይ የተንጠለጠለ ብቻም አይደለም ዕቅዳቸው። አውቀው ገብተውበትም ይሁን ተታለው የሃሳዊያን ዓላማ "የሰይጣን ዓላማ" ነው። የሰይጣን ዓላማ ደግሞ ግልፅ ነው። ወንጌልን መሸቀጥ፣ ክርስቶስን መጋረድ፣ ቤተክርስቲያንን ማዳከም፣ ሰውን ወደ ገሃነብ መስደድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ማጉደል ነው። ይኸው ነው። እኒህ ሃሳዊያን ይህንን ከክፉው የተቀበሉትን ዓላማቸውን ለመፈፀም ደግሞ በግብታዊነት አይደለም የሚሄዱት፤ ፍኖተ ካርታ (Road Map) አላቸው (ከሰይጣን የተቀበሉት)። ይህም ፍኖተ ካርታቸው አራት ደረጃዎች አሉት። እነርሱም መከላከል፣ ማጥቃት፣ መቆጣጠር እና ማሳደድ ናቸው።
የመጀመሪያው ደረጃ - "መከላከል"
በሃሰዊያኑ ፍኖተ ካርታ መሠረት የመጀመሪያው ደረጃ ስሁት አስተምህሯቸውንና ስሁት ልምምዳቸውን በተለያዩ መንገዶች ወደ አማኙ ማህበረሰብ ማስረፅ ነበር። ይህንን ለማሳካት አሳች እየተባሉም (እየተተቹም) ቢሆን ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት ብዙ ጥረት አድርገዋል። በዚህ ስራቸውም ጥቂት የማይባል ቁጥር ያለው "አማኝ" ለማጥመድ ችለዋል። ሃሳዊያኑ በዚህ በመጀመሪያው ደረጃ ወቅት በአብዛኛው "መከላከል" ላይ የተመሰረተ ስትራተጂ ነበር የሚከተሉት።
ሁለተኛው ደረጃ - "ማጥቃት"
ሃሳዊያኑ በዚህ ወቅት ሁለተኛው ደረጃ ላይ ናቸው። ይህ ደረጃ የ"ቅይጣዊነት" ደረጃ ወይም "የገፅታ ግንባታ" ይባላል። ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረዋል ማለት ነው። አሁን ዋና ትኩረታቸው ራሳቸውን ከነባሩ ክርስትና ጋር "መቀየጥ" ላይ ነው። ይህንንም ለማሳካት ከሰማይ በታች ያለውን ዘዴ ሁሉ ተጠቅመው ንፁሁን "ወንጌል" በሃሳዊ ትምህርታቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየበከሉት ይገኛሉ። በወንጌላዊያን መካከል ስለ እነርሱ የነበረውን ምልከታ "በጎ" (Positive) እንዲሆን ለማድረግም እየለፉ ነው። በተወሰነ ደረጃም እየተሳካላቸው ይመስላል። ሰሞነኛው የኡበርት ኢንጅልስን መምጣት ተከትሎ የታየውም ሁኔታ "የማጥቃት" ስትራተጂያቸው መልክ እያየዘ እንደሆነ ማሳያ ነው። ካውንስሉም ሆነ ህብረቱ ምንም ማድረግ የማይችልበት ደረጃ ላይ ነበሩና። ቅቡልነታቸው አድጓል ማለት ነው። ማወቅ ያለብን ጉዳይ እንደ ወንጌላዊያን አማኞች ከባድ አደጋ ውስጥ መሆናችንን ነው። ሃሳዊያኑ ይህንን ሁለተኛውን ደረጃ ሲያጠናቅቁ በፍጥነት የሚሻገሩት ወደ ሶስተኛው ነውና።
ሶስተኛው ደረጃ - "መቆጣጠር"
ሶስተኛው ደረጃ የመቆጣጠር ደረጃ ነው። ምን ማለት ነው? "ወንጌላዊው ክርስትና ሙሉ ለሙሉ በእነርሱ ትምህርት የሚወከልበትን ክበብ መፍጠር" ማለት ነው። በዚህ ወቅት ዋነኛ ትኩረታቸው እንደ ካውንስሉ ያሉ ተቋማትን መቆጣጠር ህብረቱንም ጥርስ የሌለው አንበሳ እንዲሆን ማድረግ ነው (ሰሞኑን እንዳየነው ማለት ነው)፤ እንዲሁም በራሳቸው ልክ ሰፍተው ያዘጋጇቸውን ማህበሮች "ተፅዕኖ ፈጣሪ" ወደሚሆኑበት ደረጃ ማሳደግ ነው። ይህ አሁንም በጥቂቱ የሚታይ ቢሆንም በአብዛኛው ግን ወደፊታዊ ነው። ይህም ደረጃ የ"መቀየጥ" ሩጫቸውን ሲጨርሱ የሚገቡበት ይሆናል ማለት ነው።
አራተኛው ደረጃ - "ማሳደድ"
አራተኛው ደረጃ የከፋው ደረጃ ነው። ሃሳዊያኑ ሙሉ በሙሉ ካውንስሉን እና መሰል ተቋማትን እንዲሁም በቀደሙ "አባቶቾ" ተይዘው የነበሩትን "የተሰሚነት መድረኮችን" መቆጣጠር የሚችሉበት ይሆናልና። እስኪ አስቡት ተስፋዬ ጋቢሶን እንደ አባት የሚቆጥር ትውልድ አልቆ ጃፒና ተዘራን "መንፈሳዊ አባት" ብሎ የሚጠራ ትውልድ ሲፈጠር። ይህ ጊዜ እውነተኛውን ወንጌል በሙሉ ሀይላቸው ማሳደድ የሚጀምሩበት ከባዱ ጊዜ ይሆናል። ይህ ጊዜ በተለይ ለእውነተኞች ጭንቅ ይሆናል። ይህ ወቅት ለሃሳዊያኑ ፍፁማዊ የበላይነትን የማረጋገጥ ደረጃቸው እና ወንጌላዊቷ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ወደ ፍፁማዊ "ጨለማ ዘመን" የምትገባበት ጊዜ ነው የሚሆነው። (እዚያ እስኪደርሱ ዝም ከተባለ)
ጊዜው አሁን ነው!
አንዳንድ ወገኖች "ሃሳዊያኑ የትም አይደርሱም.... የሆነ ወቅት መጥፋታቸው አይቀርም.... ገንዘብ ሲጠግቡ መቆማቸው አይቀርም....መንግስት አንድ ነገር ማድረጉ አይቀርም..." ወዘተ.ሲሉ ይደመጣል። አንዳንዶችም በሰሜን አሜሪካ ያለውን ተሞክሮ እያጣቀሱ "በአሜሪካን እኮ ዛሬም ድረስ በሃሳዊያኑ ያልተደፈሩ በርካታ ቤተ እምነቶች አሉ" የሚል ማስረጃ በማቅረብ ሃሳዊያኑ በሀገራችን የሚኖራቸው ተፅዕኖ ያንን ያህል አስጊ እንዳልሆነ ለማስረዳት ይሞክራሉ።
ነገር ግን ይህንን የሚሉ ወገኖች የኢትዮጵያ ወንጌላዊያንን ነባራዊ ሁኔታ ከምዕራቡ ዓለም ፈፅሞ የተለየ መሆኑን አላስተዋሉትም። ምክንያቱም በእኛ ሀገር የሚገኙ የወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት እንደ ሰሜን አሜሪካዊያኑ በቤተዕምነቶች መካከል ቀድሞውኑ የተሰመረ የልዩነት መስመር የላቸውና። በሀገራችን ቤተ ዕምነቶች መካከል ያለው ልዩነት የስምና የዲኖሚኔሽን እንጂ የአስተምህሮና የልምምድ ስላልሆነ ሁሉም አንድ ዓይነት ነው። ሙሉ ወንጌል ያለው ትምህርት መካነ ኢየሱስም፣ ቃለ ህይወትም፣ መሠረተ ክርስቶስም አለ። ልምምዱም እንደዚያው። ሰባኪዎቹም ዘማሪዎቹም ቢሆን ሁሉንም መድረክ ይረግጣሉ። ይህም ሁኔታ ደግሞ ሃሳዊያኑ ምንም ሳይገድባቸው በስህተት እርሿቸው ሁሉንም ቤተ-ዕምነቶች ለማብኳት ሰፊ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ቸል ካልነው ሳይነካካ ለዘር የሚተርፍ አንድም ቤተክርስቲያን አይኖረንም ማለት ነው።
መፍትሔው ምንድነው?
በፍኖተ ካርታቸው መሠረት በአሁኑ ወቅት ሃሳዊያኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃት (ወደ ሁለተኛው ደረጃ) ተሸጋግረዋል። ይህ ደረጃ "ቅይጣዊነት" ይባላል። ሃሳዊያኑ ይህንን ደረጃ ካለፉ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደረጃዎች ብዙም ከባድ አይሆኑም። ምክንያቱም፤ የሀገራችን አብያተ ክርስቲያናት ተቆላልፈው የሚኖሩና በመካከላቸው ምንም አጥር የሌለው መሆኑ፣ የማያስተውሉ እና "ጤነኛ" ያልናቸው "አባቶች" ለሃሳዊያን ቀኝ እጃቸውን መስጠታቸው፣ አድር ባይ "መሀል ሰፋሪዎች" ለጥቅማቸው ሲሉ "እውነትን" መሸጣቸው ለሃሳዊያኑ ስትራተጂ የበለጠ ምቹ መደላድል ፈጥሮላቸዋልና።
ስለዚህ "ያገባናል!" የምንል ሁሉ የፍፃሜው ጦርነት መሆኑን አስተውለን ለሰበብ የሚተርፍም ጊዜ ስለማይኖረን ባለን ሃይል ሁሉ ስህተትን እና ሃሳዊያንን ቀያጮቹንም ጨምሮ ለማጋለጥ እንትጋ፣ ንፁህ የሆነውን ወንጌል ለማስተማር እና ለመጠበቅ፣ ለትውልድም ለማሻገር እንጋደል፣ የሚል ጥሪ በታላቅ ትህትና ለማቅረብ እወዳለሁ። እኛ በዚህ ልክ ብንቆም እግዚአብሔርም ለእርሱ የሆኑትን ያስመልጣል።
የፍፃሜው ጦርነት ነውና! ወንጌልን ለትውልድ ለማሻገር እንጋደል!
“የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም” (ገላ 2፥5)
ቴዎድሮስ ተጫን
Gold Mafia Aljezera's documentary https://youtu.be/_qNib3Jtoc0?si=t3hEV4P5MvQTcWla
Читать полностью…የክርስቶስ መስቀል ያስገኘልን ድነት፣ ብርሃን፣ ዕርቅና ሰላም ለምድራችን ይሁን! ዳዊት "የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፣ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን።" በማለት እንደ ዘመረው፣ 2016 የሰላም ብርሃን የምናይበት ዓመት ይሁንልን።
እውነተኛ ሰላም ከክርስቶስ ማነነትና ሥራ ሊለይ አይችልም። እርሱ በመስቀሉ ላይ ሰላምን አመጣ። ክርስቶስ መጨረሻ፣ ምትክ የሌለውና ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መገለጥ በመሆን፣ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም ሰላም ሆኗል ስንል፣ ኀጢአት ያቆማቸው የጥል ግድግዳዎች መፍረሳቸውንና ዕርቅ መደረጉን ለመናገር ነው። (ሮሜ 1÷1-4)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በሰውና በሰው እንዲሁም በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ ለአንዴና ለዘላላም በማፍረስ አንድ አዲስ ሰው ፈጥሯል።
“. . . ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ [በአይሁድና አሕዛብ መካከል] ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና” (ኤፌ. 2፥14-15)። አይሁድ፣ አሕዛብ፣ ወንድና ሴት፣ ነጻና ባሪያ በክርስቶስ አንድ ሆነዋል።
በምድር ላይ ካሉ ማኅበረሰቦች ሁሉ፣ የክርስቶስን ማኅበረሰብ ልዩ የሚያደርገው ይኸው በመስቀሉ ሥራ ብቻ የተገኘው ማንነት፣ ሰላምና አንድነት ነው። ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሆኗልና! “ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተሰብ አባል” (ኤፌ 2፥19)። ይህ እግዚአብሔራዊ ቤተሰብነት፣ በየትኛውም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዐውድ የማይገረሰስ ነው።
በመስቀሉ ላይ ከተከናወነው የቤዝዎት ሥራ የተነሣ የክርስቶስ ማኅበረሰብ መታወቂያውም ሆነ ውቅሩ ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ መደብ ወይም ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም አይደለም። ስለዚህም የክርስቶስ ማኅበረሰብ መስተጋብሮች ሁሉ የሚቃኙት በክርስቶስ ባገኘው ማንነት ብቻ ነው። የዚህ ማኅበረሰብ ውበቱ ልዩነቱ ነው። ለእግዚአብሔር ለራሱ "የተለየ ሕዝብ" በሆነበት መጠን ያህል ብቻ ነው ለሌላው ሕዝብ የዕርቅና ሰላም አማራጭ መሆን የሚችለው። በርግጥ ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሆንን፣ የሚገዛንም ዋናው ፋይዳ ደግሞ ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ የተዋጀንበት ማንነት ከሆነ፣ እርስ በእርስም ሆነ ሌሎችን በብሔርተኝነት መነጽር ልንመለከት አንችልም (ራእ 5፥ 8-10)።
ብርሃነ መስቀሉን ስናከብር፣ ቤተ ክርስቲያን የታረቀች አስታራቂ የክርስቶስ አማራጭ ማኅበረ ሰብ መሆኗን በማሰብ ሊሆን ይገባዋል። ክርስቶስ በማስታረቅ ሥራው፣ በሰማይና በምድር፤ በእግዚአብሔርን በሰው መካከል በመስቀል ላይ እንደ ደቀቀ፤ ቤተ ክርስቲያንም ከመስቀሉ መንገድ ውጭ እውነተኛ የሰላምና የዕርቅ አማራጭ መንበር መሆን አትችልም።
ከትርክት፣ ከቂም እስረኝነት፣ ከአለመተማመን፣ ከክፍፍል፣ ከጥላቻና ከእርስ በእርስ መወጋገድ ጋር የተለወሰው የአገራችን ብሔር-ተኰር ፖለቲካ እጅግ በከረረበት በዚህ ወቅት፣ ቤተ ክርስቲያን በእውነተኛ አማራጭነት ታራቂ-አስታራቂ ልትሆን ተጠርታለች። የዕርቅና የፈውስ መንበር መሆን የምትችለው በመሰቀሉ ብርሃን እስከኖረች ድረስ ብቻ ነው። የክፍፍል ሰለባ ሆና፣ ሌሎችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም እርስ በእርስ ታረቁ ብላ ለመመስከር ዐቅም አይኖራትም።
የመስቀሉ እውነት ያደሰን፤ ያስገኘውም ሰላም በልባችን ይንገሥ፤ ብርሃኑም በምድራችን ላይ አብዝቶ ይብራ።
አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)