tfanos | Unsorted

Telegram-канал tfanos - Tesfaab Teshome

2111

ለአስተያየት @jtesfaab ላይ ይፃፋልኝ ለመቀላቀል @tfanos ይጫኑ። ቤተሰብ ስለሆንን አመሰግናለሁ ❤❤😍

Subscribe to a channel

Tesfaab Teshome

"ሰውዬው ክፍል ሦስት"
* * *


በሁለት እጆቹ ፊቱን ሸፍኖ ተንሰቅስቆ ሲያለቅስ ሰውነቱ ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ "ሰው መሆንህን ተጠራጠርኩ" አልኩት፡፡ የፊቱን እንባ እየጠረገ ቀና ብሎ ተመለከተኝ፡፡
"የሰው ልጅ በዚህ መጠን ለሌላ ሰው የሚያዝን አይመስለኝም ነበር" ስለው ፈገግ ሊል ሞከረ፡፡
ከመገርጣቱ የተነሳ አጥንቶቹ በሚታይበት ፊቱ ላይ የሚነበበውን ሃዘን በፈገግታው ለመሸፈን የሚታገል መስሎ ተሰማኝ፡፡

"ለማንኛውም ቢበቃን ይሻላል" ይህን ስናገር ራሱን በአሉታ ነቀነቀ፡፡ የተሸነታተረ ከናፍሩን አላቆ "ታሪክሽን ንገሪኝ" አለኝ፡፡
"የኔ ታሪክ የህመም ታሪክ ነው፡፡ ህመሜ ደግሞ ስቃይ የተሞላበትን ሃዘን ይፈጥርብሃል"
"ግድ የለሽም ያንቺን ስቃይ የመቀበል ግዴታ አለብኝ፡፡ ግዴታ!"
"እ" አልኩት በግራ መጋባት
"አዎ ስቃይሽን መቀበል ይኖርብኛል ይህ ግዴታዬ ነው"
ቀና ብዬ አየሁት። የፊቱ እንባ በመዳፉ ለማስወገድ ሞከረ።

"ሳምራዊት"
"እ" ተደናበርኩ
"ንገሪኝ። የሚሰማሽን ሁሉ ንገሪኝ"
"ህሙም ልብ ነው ያለኝ። ስሜቴ በመከራዬ ጅራፍ የቆሰለ ነው። አእምሮዬ የተሰቃዬ ነው..... ምን ነግርሃለው? የምነግርህ ሁሉ ስሜትህን የሚያደፈርስ ነው"
"መከራሽን መቀበል ግዴታዬ ነው!... ግዴታ!!"

ሳግ በተናነቀው እና ለቅሶ ባወፈረው ድምፁ ውስጥ እርግጠኝነት አለ፡፡
ላለመዋሸት ባወራሁት ቁጥር የሆነ አይነት እርካታ ይሰማኛል፡፡ የተሸከምኩትን ቀንበር እየጫንኩበት እንደሆነ ባውቅም አውርቼው ነፃ መሆንን ፈለግኹኝ፡፡

"በአባቴ የተደፈርኩኝ ቀን ነበር ከቤተሰብ የኮበለልኩት" አልኩት ተረጋግቼ፡፡
".... እንጀራ አባቴ ከተጫወተብኝ በኋላ ብር ወርውሮልኝ ሄደ፡፡ የሰጠኝ ብር ከብልግናው እኩል አሳመመኝ፡፡... ለግማሽ ቀን ስነፋረቅ ከቆየሁኝ በኋላ አመሻሽ ላይ የሰጠኝን ብር ይዤ ከቤት ወጣው፡፡ የት እንደምሄድ አላውቅምና ዝም ብዬ ተጓዝኩ፡፡ ብዙ ከተጓዝኩ በኋላ አንዲት ሴት አገኘችኝ፡፡ 'የኔ ልጅ' የሚል ድምጿን ስሰማ ቁጣና ሀዘን አስለቀሰኝ፡፡ እየደጋገመች 'የኔ ልጅ ምን ሆነሽ ነው?' ትለኝ ነበር፡፡..... ምን ብዬ ልመልስላት? ተደፈርኩ ልበላት? ህልሜን ተቀማው ልበላት? ምን ልበላት? አባቴ አነወረኝ ልበላት? ምንም የምላት ስላልነበረኝ አለቀስኩ ከእንባ ውጭ ምን ነበረኝ?..."

"...ያን ለሊት ሴትዮዋ ወደ ቤቷ ወሰደችኝ፡፡ ታምነኛለህ? በተነጠፈልኝ ፍራሽ ላይ ተኝቼ ለሊቱን ሙሉ እንባዬ ሲወርድ አደረ፡፡ ለደቂቃ እንኳን ማልቀስ ማቆም አልቻልኩም ነበር፡፡ ጥፍር ሲነቀል የሚሰማው ህመም አይነት እየተሰማኝ አለቀስኩ፡፡ታዲያልህ ሲነጋጋ ሴትዮዋንና ደግ ቤተሰቦቿን ሳልሰናበት ትቼ ወጣው፡፡"

በደቃቅ እጆቹ ጉልበቱን አቅፎ በቦዘዙ አይኖቹ እየተመለከተኝ ነው፡፡
ድንገት ወሬዬን ገትቼ "ለምን እንደምነግርህ ታውቃለህ?" ስለው ራሱን በአዎንታ ነቀነቀ፡፡
"እውነት ታሪኬን ለምን እንደምነግርህ ታውቃለህ?"
"በእርግጠኝነት አውቃለሁ" ድምፁን ሃዘን አሻክሮታል፡፡
"እሺ" አልኩና መተረኬን ቀጠልኩ፡፡

"ባገኘሁት መኪና ተሳፍሬ ከተማዬን ለቅቄ ሄድኩ፡፡.... በማለውቀው ከተማ በግርድና ተቀጥሬ መስራት በጀመርኩበት ወቅት ነው ያ የአንሶላ ሞዴስ ታሪክ የተፈጠረው፡፡ ቀጣሪዎቼ ደሞዜን እነርሱ ጋር እንዳጠራቅም ሲጠይቁኝ አልተከራከርኳቸውም፡፡ የምሟገትበት አቅምም ፍላጎቱም አልነበረኝም፡፡ የሚገርምህ የቤት ሰራተኛ ሆኜ የምሰራላቸው 'ሰው' መሆኔን የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡.... ማሽን ይመስል ያለ መድከም ማገልገል ግዴታዬ ነው፡፡ ለሊት እነሳለሁ፡፡ አርፍጄ እተኛለሁ፡፡ የንፅህና ጉዳዬ ግድ አይሰጣቸውም፡፡ ሞዴስ እንደሚያስፈልገኝ አይገነዘቡም፡፡ ስለዚህ የአንሶላ ጨርቅ እንደሞዴስ ተጠቀምኩ:: ጉልበቴን እንደባሪያ የምገብር ገረድ መሆኔ ሳያንስ በሴትነት ግዴታዬ ወቅት የአንሶላ ጨርቅን ተጠቀምኩኝ"

(ክፍል አራት ይቀጥላል


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

አምስት ፅሁፉ እንዲቀጥል የሚፈልግ ሰው ካለ እቀጥላለሁ

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

"መንገዳችን......"
* * *

አባት ሆይ፥
አብረሃም ለሳራ ፥ሄዋንም ለአዳም፥
ካንተ ዘንድ ሲሆኑ
ስንት'ዜ በርትተው ፥ ስንት ጊዜ ሳቱ
ስንት ጊዜስ ባከኑ??
ስንት ጊዜ ተነስተው፥ ስንት ጊዜ ወደቁ
እንደምንድን ኖረው ፥ እንዴትስ ፀደቁ?

የንጉስ ዳዊት ልጅ ፥ አንድ ሺህ ሲያገባ
ስንት ጊዜ ስቆ ፥ ስንት'ዜስ አነባ
ጎልያድን ያህል ፥ በወንጭፍ የጣለ
የንጉስ ዳዊት ልብ ፥በሜልኮል መነሻ
ስንት ጊዜ ዛለ?

እኔ እንደሆንኩ:-
ይህ ትንሽ ልቤ ፥አንተ የሰራሃትን
ኢምንት የከጀለ
እርሷን ጣኦት አ'ርጎ ፥አምላኩን ገ ደለ


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

አብይ ግድብ ተገድቦ ሲያልቅ ግድቡ ያለበት ክልል ቢገነጠልስ? እንደው በሆነ መንገድ ወደብ ብናገኝና ወደቡ ያለበት ክልል ቢገነጠልስ?

አሁን ባለው ሁኔታ ክልሎች እጩ ሐገራት ናቸው። የሆነ ቀን ከመኝታችን ስንነሳ ሐገር ሆነው ይጠብቁን ይሆናል።

ከግዜ ወደ ግዜ ብሔራዊ ስሜት እየሞተ ነው። በአንፃሩ ብሔርተኝነት ገንግኗል።

ጋምቤላ በደቡብ ሱዳን አማፂያን ሲጠቃ መንግስት ሊከላከለው አልሞከረም። አልሸባብ ሱማሌን ሲያተራምስ ፌደራል መንግስት ጆሮ ዳባ ብሏል። ሱዳን በአማራ ክልል በኩል ስትገባ መከላከያ ቸል ብሏል። ኤርትራ ደግሞ በመንግሥት ግብዣ ትግራይን ወራለች።

መንግስት ለሉአላዊነት የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታ ክልሎች 'ኢትዮጵያ በቃችን' ላለማለታቸው ምንድነው ማረጋገጫው?

በየሄዱበት ባይተዋር የተደረጉ ዜጎች ፥ በማንነታቸው የተጠቁ የተሳደዱ እና የተገደሉ ዜጎች "ከኢትዮጵያ ተገንጥለን ራሳችንን የቻልን ሐገር ካልሆንን በቀር ራሳችንን ማዳን አንችልም" ብለው ቢገነጠሉስ?

በግልፅ አማርኛ ፥ ኢትዮጵያ የመፍረስ ስጋት አለባት። ይሄን ስጋት በአግባቡ ተረድቶ ለመፍትሔው ከመስራት ይልቅ "ኢትዮጵያ አትፈርስም" በሚል ምናብ ወለድ ፕሮፖጋንዳ ህዝብ ለማደንዘዝ ይሞከራል።

በዚህ ሁኔታ ዜጎች ለብሔራዊ ጥቅም አይደለም ህይወት ገንዘብ ለመስጠት ባይፈልጉ ይፈረዳል ?

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ከሞትክ በኋላ ምን ትሆናለህ?
* * *

ዝርዝር ድርጊቶቻችን ከዋናው አስተሳሰባችን ይቀዳሉ። ግንዛቤያችን የእለት ተዕለት ኑሯችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።
ከሞት በኋላ ስለሚሆነው ነገር ምን ታስባለህ?
የድህረ ሞት አስተሳሰብ በግለሰቦች ባህሪ ፥ በማህበረሰብ እሴት ፥ በህዝብ ባህል ፥ በሐገራዊ ምልክቶች ላይ ጭምር ተፅዕኖ ያሳድራል።

ሳይኮሎጂ ቱደይ ድህረገፅ "How Do Your Afterlife Beliefs Affect Your Daily Life?
The life you imagine after death manifests subtly in your life now" በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ ያስነበበ ሲሆን 'ሞትን ተከትሎ ምን ይመጣል?' የሚለው አስተሳሰብ እንዴት ባለ መንገድ ባህሪን እንደሚገራ አብራርቷል።

ድህረ ገፁ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ እንዳብራራው ከሆነ፥ ሞትን ተከትሎ ስለሚመጡ ነገሮች ያሉ እምነቶች ተፅዕኗቸው የሰፋ ነው። በአካባቢ ጥበቃ ፥ በብሄራዊ ማንነት፥ በጥላቻ እና ፍቅር ፥ የስሜት ደረጃዎች ወዘተ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

ከሞት በኋላ ህይወት እንደሚቀጥል ማመን ስለ ሕልውናችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እርግጠኛ አለመሆንን ከመቀነስ በተጨማሪ የሞት ፍራቻ ጭንቀትን ያቃልላል ተብሏል።

ከሞት በኋላ ህይወት እንደሚቀጥል ማመን በአከባቢ ጥበቃ ላይ የራሱን ተፅዕኖ ያሳድራል።
በተለይ የምስራቅ እምነቶች ፥ ሰዎች ከህልፈት በኋላ ዳግመኛ ወደ ምድር እንደሚመለሱ ያስተምራሉ። ይህም ተፈጥሮን እንዲንከባከቡ ያደርጋቸዋል።
በተቃራኒው ከሞት በኋላ እስከመጨረሻው ምድርን ለቀው እንደሚሄዱ ሪፖርት ያደረጉቱ በአከባቢ ጥበቃ ላይ ተሳትፎ የማድረግ ዝንባሌያቸው ዝቅተኛ መሆኑ ተስተውሏል።

አስገራሚው ነገር ድህረ- ሞት ግንዛቤ ብሔራዊ ማንነት ላይ ተጽእኖ ማሳደር መቻሉ ነው።

በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣር 2021 ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው ሰዎች ከህልፈት በኋላ ምን እንደሚከተል ያላቸው እምነት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከብሄራዊ ማንነት ጋር ቁርኝት አለው።
ስለሞት ያለ የወል ግንዛቤ ልማድ እና እሴት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የዳበረ ንፅረተ አለምን የሚፈጥር ሲሆን ይህም በብሔራዊ ባህል ላይ የራሱን አሻራ ያኖራል።

ድህረ ሞት አስተሳሰብ፥ ስሜት ላይ ብርቱ ተፅዕኖ በማድረስ የጥላቻ እና ፍቅር አቅጣጫን የመግራት አቅም አለው።
የምናገላቸው እና የምነቀበላቸው ልማዶች ላይ ፥ ለድርጊቶች የሚሰጥ ብያኔ፥ ፍርድና ይቅርታ፥ ወግ አጥባቂነት እና ተራማጅነት ሁሉ ስለሞት ካለ ግንዛቤ ጋር የሚዛመዱበት መስመር አለ።


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ልህቀት
(ድጋሚ የተፖሰተ)
* * *

ማኪያቶን ተመልከት፣
ወተት በቡና ነው፥ ከጥቁር ከነጩ፥ የተቀላቀለ
ተቃርኖ አፅናፍን፥ ዋልታዎች ያዘለ
ወተትን ያልሆነ ፥ቡናንም ያይደለ

ይልቅ፣
ከወተት መንጣትን፥
ከቡና ጥቁረትን ፥
በአንድ የደባለቀ
ሁለቱን ያልሆነ ፥ከመምሰል የላቀ
በብዝሃ ፍቅር፣
በልዩነት እውነት፥ እጅግ የረቀቀ
መክሰልን ከ መንጣት ፥በአንድ የደባለቀ፤

እጅግ የነጠረ ፥አንዳንድ ላቂ አለ
ከልዩነት መሃል፥ ሐቅን የከፈለ
ማንንም ያልሆነ
ከሁለት መልኮች ወ'ቶ ፥ሁለቱን ያይደለ
ውልደ ጥምር ሳለ ፥ ራሱን የመሠለ፥
ራሱን የወከለ
አንዳንድ ላቂ አለ፡፡


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

"ልጠይቅህ"
(ተስፋኣብ ተሸመ)

በመንበርህ፥ ተሰይመ
በዙፋንህ ፥ ተደላድለ
ኹሉ በእጅህ፥ ሆኖ ሳለ
ልብህ ለግፍ ፥ ተቻኮለ ፤

ፈገግታዬን ፥ ልትቀማ
ማጉረምረሜን ፥ ልትሰማ
ያለመጠን ፥ በርትተኻል
እንዳነባ ፥ ታትረኻል፤

ልጠይቅህ?
ፍስሃዬ፥ እንዲከስም
ድብዝዝ ቀኔ፥ እንዲጨልም
ትጉ መሆን ፥ ምን ይባላል?
ፅዩፍ ድርጊያህ ፥ ያኮራሃል?

ልጠይቀህ

ብሩህ ጀምበር ፥ ያጠለቀ
ፋኖስ ኩራዝ ፥ ከነጠቀ
መጠለያ ፥ ያፈረሰ
መታጎሪያ ፥ ከቀለሰ
የእንባ ጎርፍን ፥ የፈጠረ
ያለቀሰን ፥ ካነወረ
ነፃነትን ፥ የጨቆነ
የተከፋን ፥ ከኮነነ
ባርነትን ፥ የፈጠረ
በድል ስሜት ፥ ከፎኮረ

ይኽ ሁሉ ፥ በምን አግባብ ፥ ይመዘናል?
ነውር እንደ ጌጥ ፥ ይጠቀሳል?

(ከረሳኸው)

መሳቅ ሲያርህ፥
ፈገግታዬን ፥ ቀምተኻል
መፍካት ሲያሻህ፥
የኔን ፀሐይ፥ አክስመኻል
ልጠይቅህ፥ የከወንከው፥ ያኮራኻል?


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ልጅስ በመታሰሩ እንኳ ደስ ያለሽ
* * *

"ልጅሽ የት ነው?"
"እስር ቤት"
"እንኳን ደስ ያለሽ"
"በአምላክሽ"

ይህ ተራ ቀልድ መስሎ ቢታይም በአንድ ዘመን በሐገራችን ሰማይ የነበረን ሁኔታ ገላጭ ነው።
በመልአከ ሞት የሚመራ የሚመስለው ፖለቲካችን በሰበብ አስባብ ሞትን ያመርታል። በፖለቲካ ሰበብ፥ ወጣቶች በጉብዝና ዘመናቸው ወደመቃብር ተሸኝተዋል፥ አዛውንቶች ለክብረነክ አሟሟት ተዳርገዋል፥ ጎልማሶች እንደወጡ ቀርተዋል፥ ጎረምሶች በአበባነት ዘመናቸው ተቀጥፈዋል።
ፖለቲካ ሞትን በሚያመርትበት ዘመን መታሰር እድለኝነት ነው።

ታላቁ የታሪክ መርማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ "ህብር ህይወቴ" በሚል ርዕስ ግለታሪካቸውን አስነብበውናል። መፅሐፉ እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው ሁሉም ሰው ሊያነበው የተገባ ግሩም ስራ ነው።

ፕሮፌሰር ባህሩ በወጣትነቱ በእንግሊዝ ሐገር ዶክትሬቱን ከተማረ በኋላ ማመንታቱን አርቆ ስጋቱን አሸንፎ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ ወሰነ። ያኔ በአብዮት ሰበብ ሽብር የተንሰራፋበት ስለነበር ባህሩ ወደ ኢትይኦጵያ መምጣት አስግቶት የነበረ ቢሆንም "ሐገሬን ማገልገል አለብኝ" በሚል ውሳኔ ሐገሩን ሊያገለግል ወደ ኢትዮጵያ መጣ።

ሐገር ቤት ገብቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተቀጠረ 3ኛ ሳምንት ቢሮው ተንኳኳ።

"ዶክተር ባህሩ ነህ?"
"አዎ ነኝ"
"ለ 5 ደቂቃ ደርግ ፅህፈት ቤት ትፈለጋለህ"
"ታዛዥ ነኝ"

'የሐገሬ ውለታ አለብኝ' በማለት ከእንግሊዝ ሐገር ወደ ሐገር ቤት የመጣው የታሪክ ዶክተር 'ለ5 ደቂቃ ትፈለጋለህ' ተብሎ ተወስዶ አምስት አመት ያለ ፍርድ ታሰረ።
ለእስር የሚያበቃ ወንጀል አልሰራም። እንደዋዛ 5 አመታት በእስር ካሳለፈ በኋላ "ነፃ ነህ" ተብሎ ተለቋል።

አንድ ቀን ባህሩ መርማሪ ዘንድ ቀረበ። መርማሪው የተለያዩ ጥያቄዎችን ከጠየቀ በኋላ ባህሩ "ወደ ኢትዮጵያ መምጣቴ ስህተት ነበር፥ ይኸው ታሰርኩ" አለ በምሬት።ይሄኔ መርማሪው "እንዲህማ አትበል። በመታሰርህ አትማረር፥ መታሰርህ እድለኝነት ነው" አለው።

አዎን፥ መታሰር እድል ነበር። ያኔ ለእስር ካልተዳረጉት መሐከል ብዙዎች የጥይት ሲሳይ ሆነው ሞተዋል። ባህሩ በመፅሐፉ እንደመሰከረው 'ነገሮች ካለፉ በኋላ ሳስበው መታሰሬ እድል ነበር፥ ከማውቃቸው ወጣቶች መካከል ሳይታሰሩ ቀርተው የሞቱ ብዙ ናቸው' ብሏል።

ባህሩ ዘውዴ 'ለ5 ደቂቃ ትፈለጋለህ' ከተባለ በኋላ እንደዋዛ 5 አመታትን በእስር አሳልፎ 'ነፃ ነህ' ተብሎ ተለቀቀ።

ከእስር የወጣ ቀን የእድል ነገር ሆኖ ዘንጦ ነበር። ነገር ግን ኪሱ ባዶ ነው።
ግራ ሲገባው መንገድ ላይ አንድ ወጣት አግኝቶ 'እባክህ 10 ሳንቲም ስጠኝ' ብሎ ለመነው። እንግሊዝ ሐገር ዶክትሬቱን ተምሮ የመጣው ባህሩ ዘውዴ አስፓልት ዳር ቆሞ አስር ሳንቲም ለመነ።

"ኅብር ህይወቴ" በሚለው ግለታሪክ መፅሐፍ መነሻችን ላይ ያለውን ጭወውት የሚገልፅ ነገር ሰፍሯል።

"በዛ የጭንቅ ዘመን እናቶች ሲገናኙ 'ልጅዎ እስከአሁን እስር ቤት ነው?' ይባባላሉ። 'አዎ እስር ቤት ነው' ከተባለ በጣም ጥሩ ነገር ነው" ይላሉ በማለት አስፍሯል።

ያኔ፥ ከእስር ውጭ ሆኖ የጥይት ሲሳይ ከመሆን መታሰር የተሻለ ነበር


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ስማችን የፖለቲካ አቋማችንን የሚያስረዳበት ዘመን ላይ ደረስነ

ቶሎሳ፥ ዴምለው፥ ሀጎስ ፥ ሀሰን ፥ ኢሳያስ .... ወዘተ ከስማቸው ተነስተን የፖለቲካ አቋማቸውን ቀድመን ልንረዳ የምንችልበት ግራ አጋቢ ሁኔታ ተፈጥሯል

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

የአንድ ማህበረሰብ እውነተኛ መልክ ያለው በዝነኞቹ ውስጥ ነው። በጣም ዝነኛ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች የህዝቡን ስነልቦናዊ ውቅር፥ ማህበራዊ ፍልስፍና ወዘተ ገላጭ ናቸው ብዬ አስባለሁ።

እኛ ሐገር የዝና ማማ ላይ የወጡት እነማን ናቸው?

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ሀ፥ ታሪክ አጣቅሰን ታላላቆችን ማድነቃችን መልካም ነው። ነገር ግን ጦረኞችን የምናደንቀውን ያህል አሰላሳዮችን አለማድነቅ ልክ አይደለም። ለአርበኛ በላይ ዘለቀ የቀረበው ውዳሴ ሩብ ያህል ለፈላስፋው ዘረአያዕቆብ አልቀረበም። ስለአብዲሳ አጋ በምንናገርበት ልክ ስለ ገብረህይወት ባይከዳኝ አንናገርም። ለተኳሽ የምናንፀውን ሀውልት ለ አሰላሳይ አንፈቅድም። ጦረኛ እንጂ ፈላስፋ አናከብርም። ይህ ልክ አይመስለኝም።

ለ፥ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ታላቅነት ብዙ ተብሏል። ከቴዎድሮስ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ትዕምርት የመቅደላ ገድል ነው። ክፋት የለውም። ነገር ግን ከመቅደላ በላይ የጋፋት ታሪክ ጎልቶ ቢነገር ጥሩ ነበር። ከተዋጊው ቴዎድሮስ ይልቅ ቴክኖሎጂ አፍቃሪው እና መሳሪያ ፋብሪካ እንዲኖረው የተመኘውን ቴዎድሮስ ማግነን ሸጋ ይመስለኛል።

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

12 ሰኣት አአባቢ ስልክ ተደወለልኝ። ደዋይዋ እናቴ ናት። "ዳዊት ታሞ ሃኪም ቤት ነን" አለችኝ። ሺ ነገር እያሰብኩ በጥድፊያ ሃኪም ቤት ሄድኩ። ቤት ውስጥ አራት ልጅች ነን። አራታችንም ወንዶች ነን። እኔ የመጀመሪያ ዳዊት የመጨረሻ። ሲወለድ ስም ያወጣሁለት እኔ ነኝ።

ሰምኑን አራታችንም የቤቱ ልጆች ታመናል። እኔ የጨጓራ ቁስለት ታናሼ ከሚሰራበት ወድቆ የእጅ ስብራት የሱ ታናሽ ወባ።

ዳዊት ያለበት ሃኪም ቤት እስክደርስ ከባጃጅ ሾፌር ኤቲኤም ለማውጣት ከተሰፉ ሰዎች ከሆስፒታሉ ጥበቃ ተጣላሁ።
በጣም ፍርሃት ውስጥ ሆኜ ደረስኩ።

ድንገተኛ ክፍል ተኝቷል ስባል ሺ ነገር አሰብኩ።
ወደ አእምሮዬ የሚመጣው ሁሉ መጥፎ ነገር ብቻ ነው።

በዘመኔ ለዳዊት እና ለምህረት (እናቴ) አንድ ነገር ማድረግ ስመኝ ነው የኖርኩት።

በብርድ ሰኣት አላበኝ ዛሬ። ምንም የማይጠቀም ነገር ሳደርግ ነው የቆየሁት።

ነርሷ ገር እና መልካም መሆኗ ቢያረጋጋኝም በአእምሮዬ ብዙ መጥፎ ነገር አሰብኩ።

ችግሬን በሶሻል ሚዲያ ማጋራት ቀርቶ ለጓደኞቼም የመናገር ልምድ የለኝም። ብዙ ነገሮችን ውጬ አልፋለሁ።
ዛሬ ግን ለብዙ ሰው በደቂቃዎች እድሜ ደወልኩ።

እንዲህ ተሳቅቄ አላውቅም

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ፌስቡክ ላንተ ምን አይነት ነው?

ፌስቡክ ስትገባ ጋጠወጥ ነገር ይበዛል ? ተሳዳቢ ፥ ሌሎችን የሚያዋርዱ ፥ ሰዎችን ማክበር የማያውቁ ፥ በሰው ቁስል እንጨት በመስደድ የሚደሰቱ ሰዎች የታጨቁበት ነው?

ፌስቡክ ላንቺ ምንድነው?

ሐሜተኞች ፥ ጨለምተኞች ፥ በሰው ውደቀት ፍስሃ የሚያገኙ ፥ በሌሎች ስኬት የሚቀኑ ፥ አሉታዊ ሰዎች የታጨቁበት ነው?

ፌስቡክ ለናንተ ምንድነው?

ተራ ቧልት ፥ የማይረባ ቀልድ ፥ ክብረነክ ጨዋታ የታጨቀበት ነው?

እውነት መስሎ ባይታየንም ማህበራዊ ትስስር ገፆች ማንነታችንን የሚገልፅ መስታወት ጭምር ናቸው።

ፌስቡክ የሚሰጠን የምንፈልገውን ነው። ልባችን ባለበት በዚያ የፌስቡክ መልክ አለ።

በዙሪያችን ያሉ ሁሉ ሃሜተኛ ሲሆኑ ራሳችንን መጠርጠር አለብን። ለሃሜት የሚመች ዝንባሌ ከሌለን በቀር በሃሜተኞች አንከበብም።

ፌስቡካችን በማይረባ ነገር የተሞላ ከሆነ ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። ፌስቡክ ገበያ ቢሆን ፖስቶች ሸቀጥ ናቸው። ሻጭ ካለ ፈላጊ አለ።

ሾልከው የሚገቡ ጥቂት የማይረቡ መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የፌስቡካችን ዋና መልክ የማይረባ ነገር ከሆነ አንዳች ስህተት ሰርተናል። የማይረባ ነገር እያደንን ነው ማለት ነው።

በፌስቡክ ንግድ አለ፥ በፌስቡክ እውቀት አለ፥ መረጃ አለ፥ ጓደኝነት አለ፥ ፖለቲካ አለ፥ ዝሙት አለ፥ ጨዋታ አለ፥ ዘረኝነት አለ፥ ሃይማኖት አለ... ወዘተ

ፌስቡክ ላንተ ምንድነው?

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ስለጭንብላምነት
* * *

ከሆነ ወቅት በኋላ ፋሽን ከሆኑ ፖለቲካ-ቀመስ ንግግሮች መካከል አንዱ 'ጭምብላም' የሚለው ቃል ነው።
"ምርጥ ኢትዮጲያዊ" እና "ንፁህ ኢትዮጵያዊ" ሌላኛው ለስላቅ አላማ የሚውል የማሽሟጠጥ ንግግር ነው።

ሁላችንም እንደምናውቀው ከላይ የተጠቀሱት አገላለፆች ራሳቸውን እንደ ሁነኛ ኢትዮጵያዊ የሚቆጥሩ ፥ ብሔርተኝነትን እንፀየፋለን እያሉ በድብቅ ብሔርተኛ ለሆኑ ሰዎች የሚውሉ ናቸው።

በእርግጥ ባለፉት አመታት የብዙ ሰዎች ጭንብል ተገፏል። ሚዛናዊ የሚመስሉ ሰዎች ጭንብላቸው ተገፎ ግብዝነታቸው ገሃድ ወጥቷል። በአንደበታቸው ስለ አንድነት የሚለፍፉቱ ድርጊታቸው ተቃራኒ ሆኖ ታይቷል።

ነገር ግን ባለፉት አመታት የተገፈፈው የፌክ ኢትዮጲናዋያን ጭምብል ብቻ አይደለም። የፌደራሊስቱም ጭምብልም ተገፏል።

"ምርጥ ኢትዮጲያዊ" የሚባሉት ላይ የሚሳለቁቱ በተመሳሳይ "ምርጥ ፌደራሊስት" ነን ባይ ግብዞች ላይ ሲሳለቁ ተመልክተን አናውቅም።

በርካታ ፌደራሊስት ነን ባይ ግብዞች በአንደበታቸው ስለብዝሃት ፥ ስለህዝቦች እኩልነት ፥ ስለ ሃይማኖቾች መከበር ፥ ስለ አካታችነት ሲነግሩን ከቆዩ በኋላ ድንገት ጭምባቸው ተገልጦ ማንነታቸው ገሃድ ወጥቷል።

ስለ ብዝሃነት ሰብከው ሲያበቁ ጨፍላቂ ድርጊትን ደግፈው ተገኝተዋል። ስለ እኩልነት ባወሩ ማግስት ለመብት ረገጣ ድጋፍ ቸረዋል። ስለ ሃይማኖት መከበር እንዳላወሩ ሃይማኖቶች ሲጠቁ ሃሴት አድርገዋል። ስለ አካታችነት እንዳልሰበኩ አግላይነታቸው ተጋልጧል።

ባለፉት አመታት ስለ ሐገራዊ አንድነት ሲሰብኩ የነበሩ ፥ ብሔርተኝነትን ሲቃወሙ የኖሩ ጭንብላቸው ተገፏል።

ባለፉት አመታት ስለ ፌደራሊዝም የደሰኮሩቱ ፥ ስለ ብዝሃነት ያወሩቱ ጭንብላቸው ተገፏል።

"ፌክ ኢትዮጵያዊ" ከሚለው የስላቅ ንግግር እኩል "ፌክ ፌደራሊስት" የሚል ሽርደዳም ያስፈልጋል።

ጭምብላቸው የተገፈፈው የሁለቱም ካምፕ ነው !

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

"ኦሮማይ፥ ወደ ዱቄትነት የተለወጠው መፅሐፍ"
* * *

አንዳንድ መፅሐፍት ከያዙት ታሪክ የሚገዳደር ታሪክ ይኖራቸዋል። አንዳንድ ድረስቶች ባለታሪክ መሆን እድል ፈንታቸው ይሆናል። ኦሮማይ ከነኚህ መካከል ነው

ስሙ እና የአሁን ዘመን ስራው እንዲጠቀስ የማይወድ ሰው ለእንዳለ ጌታ ከበደ ስለ ኦሮማይ መፅሐፍ ሊነግረው ፈቀደ። እንዳለ የግለሰቡን ስም ላለመጥቀስ የገባውን ቃል አክብሮ "በአሉ ግርማ፥ ህይወቱ እና ስራዎቹ" በሚለው መፅሐፉ የኦሮማይን መፅሐፍ ነገር ከትቧል

ኦሮማይ ለህትመት ከበቃ በኋላ ማባራት የማይችል ውዝግብ ተፈጠረ፥ ሹማምንት ደራሲው ላይ ጥርስ ነከሱ፥ ባለስልጣናት ተቆጡ፥ አመራሮች መፅሐፉን ተፀየፉት።
ስመ ገናናው ኩራዝ ማተሚያ ቤት ቀጭን ትዕዛዝ ደረሰው። "መፅሐፉን ሰብስባችሁ በእድ ክፍል አሽጉት" ተባሉ። ከበላይ አካል የመጣ ፥ ሊተላለፉትም የማይችሉት ብርቱ ትዕዛዝ ነውና እንደተባለው አደረጉ። ኦሮማይ መፅሐፍ ተሰብሶቦ በአንድ ክፍል ታሸገበት።

መፅሐፉን በአንድ ክፍል የማጎር ስራው የተከናወነ ምሽት ስሙ እንዲጠቀስ ወደማይፈልገው የማተሚያ ቤቱ ባልደረባ መኖሪያው ተንኳኳ። ግለሰቡ በሚሽት በሩን የቆረቆረውን ሰው ለማወቅ ከነቢጃማው ተነሳ፥ ደጁን ላንኳኩት በሩን ከፈተላቸው።

ሰዎቹ ሶስት ናቸው። መታወቂያቸውን አሳዩት። የደህንነት መስሪያ ቤት ሰዎች ናቸው።
"ለስራ ጉዳይ ትፈለጋለህ፥ ልብስህን ልበስ፥ የቢሮህንም ቁልፍ ያዝና ተከተለን" አሉት። የደህንነት ሰዎችን እምቢ ማለት ራስ ላይ ሞትን መጋበዝ ስለሆነ በፀጥታ ተከተላቸው።
በመኪና ወደ ማተሚያ ቤቱ አቀኑ።

ወደ ማተሚያ ቤቱ ከደረሱ በኋላ የታሸገውን ክፍል ከፈቱ። በታሸገው ክፍል የበአሉ ግርማ መፅሐፍ ተከማችቷል። ብጣሽ ወረቀት ሳያስቀሩ አንድ በአንድ መፅሐፎችን በመኪና ጫኑ።

የማተሚያ ቤቱን ባልደረባ "ስለምታስፈልገን ግባ" ብለውት ወደ ወንጂ ጉዞ ጀመሩ

ወንጂ ወረቀት ፋብሪካ ከደረሱ በኋላ የተጫነው መፅሐፍ አንድም ሳይጎድል ከመኪናው እንዲወርድ ተደርጎ ወደ ወረቀት መክተፊያው ተወሰደ።

"የሚሆነውን አይተህ ምስክር እንድትሆን ነው ያመጣንህ" አሉት ግለሰቡን።

ግለሰቡ ቆሞ እየተመለከተ የበአሉ ግርማ "ኦሮማይ" መፅሐፍ ኮፒዎች በአንድ በአንድ ተከትፈው ወደ ዱቄትነት ተቀየሩ።

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ሰውዬው ክፍል ሁለት
* * *

እንደ እውነተኛ ወላጅ አባቴ በምቆጥረው እንጀራ አባቴ መደፈሬን ስነግረው ያኔ የተሰማኝን አይነት የነፍስ መታመም የተሰማው መሰለ፡፡ በእጁ ደረቱን እየደጋገመ ሲደልቅ ምን ያህል እንዳዘነ ገባኝ፡፡ በዚህ የተነሳ ደስ አለኝ፡፡ 'አንድ የሚያዝንልኝ ሰው አለ ማለት ነው' አልኩኝ ለራሴ እየደጋገምኩ፡፡

በ15 አመቴ መደፈሬን ለማንም አውርቼ አላውቅም፡፡ ለማንም! ቁስሌን ለሰዎች የማሳይበት አቅም ይኖረኛል ብዬ ገምቼ አላውቅም ነበር፡፡ ብችል ያንን ክስተት ከነፈጠሩ መርሳት እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ተገድጄ መደፈሬን ከአእምሮዬ የትውስታ ማህደር ማስወገድ አልችልምና ልረሳው የምፈልገውን ህመሜን በየእለቱ አስታውሳለሁ፡፡ ባስታወስኩት ቁጥር ደግሞ ነብሴ ጭምር ታለቅሳለች፡፡ የመረቀዘ ልቤ ይደማል አይኖቼ ያነባሉ፡፡ ነገሩን ባሰብኩ ቁጥር ልገልፀው በማልችለው መጠን እሸማቀቃለሁ፡፡
ዛሬ ግን ምን ነክቶኝ እንደሆነ ባላውቅም እንባ አልወጣኝም፡፡ ለማንም ልናገር የማልፈልገውን ህመሜን በተናገርኩ ቁጥር የተሰበረ ልቤ እየተጠገነ ያለ ያህል ይሰማኝ ጀምሯል፡፡
እዚህ ምድር ላይ ያለ የመፅናኛ ቃል ሁሉ ቢደመር የማልፅናና አይነት ብሆንም ዛሬ ግን ያለ ማፅናኛ ቃል መፅናናት የጀመርኩ መስሎ ተሰማኝ፡፡

እኔ ያሳለፍኩትን ስቃይ ሳወራው ያለቅሳል፡፡ ሲያለቅስ ደግሞ እንደታዘነልኝ ስለሚሰማኝ ደስ ይለኛል፡፡ 'አንድ የሚራራልኝ ሰው አለ ማለት ነው፡፡ በሽርሙጥናዬ የማይፈርድብኝ በጥፋቶቼ የተነሳ ጅራፍ ማንሳት የማይቃጣው አንድ ሰው አለ ማለት ነው' አልኩኝ ለራሴ በድጋሚ፡፡
ደረቱን ደጋግሞ ከደቃ በኋላ እንባውን ጠራረገና መራራቱን በሚያሳብቅ መንገድ ተመለከተኝ፡፡ የለቅሶ ብዛት ባቀላቸው አይኖቹ ስር ፍቅር ይነበባል፡፡
"ታውቃለህ እስኪደፍረኝ ድረስ አሸብርን እንደወላጅ አባቴ ነበር ማስበው" አልኩት
የምተርክለት ታሪኬ ህመምን እንደሚፈጥርበት ባውቅም ባወራሁት መጠን ቁስሌ የሚሽር መሰሎኛልና ለራሴ ላደላ ተገደድኩኝ፡፡
"... ታውቃለህ አሸብር እስኪደፍረኝ ድረስ እንደወላጅ አባቴ ነበር ማስበው፡፡ አንድም ቀን እንጀራ አባትነቱ ትዝ ብሎኝ ስለማያውቅ 'አባዬ' እያልኩ እጠራዋለሁ፡፡"
"... ወላጅ አባቴ ገና የ8 አመት ልጅ ሳለሁ ነበር እኔንና እናቴን ለመከራ ትቶን የሄደው፡፡ ጥሎን ሲሄድ በትንሿ ልቤ ላይ የጥላቻ ዘር ተዘራ፡፡ ወላጅ አባቴ ለመካራ ዳርጎን ስለሄደ ጠላሁት፡፡ አቄምኩበትም፡፡ ምናልባት እኮ አባቴ ትቶን እንዲሄድ ያስገደደው ምክኒያት ይኖረው ይሆናል፡፡ እኔ ግን በጨቅላነት እድሜዬ የአባቴን ምክንያት የምረዳበት አቅሙም ሰበቡም አልነበረኝም፡፡ ስለሄደ ጠላሁት፡፡ መከዳት ተሰማኝ፡፡ ዛሬ ላይ ሆኜ የትኛውም ምክንያት የወለዱ ሰዎች ትዳራቸውን ለማፍረስ በቂ እንደማይሆን እወራረዳለሁ፡፡ የትኛውም ምክንያት!"
".... አባቴ ከሄደ በኋላ ለሁለት አመታት ያህል ከእናቴ ጋር የመከራ ኑሮ አሳልፈናል፡፡ እነኛ ሁለት አመታት በስቃይ የተሞሉ ነበሩ፡፡ በነዚያ አመታት እናቴ ያላለቀሰችበትን እለት አላስታውስም፡፡ በየቀኑ ታለቅሳለች፡፡.... ያኔ ማብቂያ የሌለ የሚመስል ሃዘኗን ስመለከት በሆነ ተአምር አድጌ ትልቅ ሰው መሆንን ተመኘሁ፡፡ ትልቅ ሰው ሆኜ እናቴ እንዳታለቅስ የማደርግበትን እድል ለማግኘት ፈለግኹ፡፡...... አየህ አሸብር በዚህ ወቅት የተከሰተ አዳኛችን ነው፡፡ እሱ ወደቤታችን ሲመጣ የደበዘዘ ህይወታችን መድመቅ ጀመረ፡፡ የዘመመ ጎጇችን ተቃና፡፡ በመሸማቀቅ ብዛት ወደታች ያዘነበለ አንገታችን በኩራት ቀጥ አለ፡፡ ሠው ሆንን፡፡ አሸብር ለእናቴ ባል ለእኔ እንጀራ አባት ሆኖ ሲመጣ እንደ አዲስ ተወለድን!"
".... ለአምስት አመታት ስንኖር እንደ እንጀራ አባት ቆጥሬው አላውቅም፡፡ እንደውም የትኛውም ልጅ አባቱን ከሚወደው በላይ እወደዋለሁ፡፡.... በሂደትም አሸብር በጣም የምሳሳለትና ቶሎ ቶሎ የሚናፍቀኝ ሰው ሆነ፡፡ ያለ እርሱ መመገብ አቆምኩ፡፡ እርሱም ቢሆን ከእናቴ አንድ ወንድ ልጅን ያገኘ ቢሆንም ግልፅ በሆነ አኳኋን ለእኔ ያደላ ነበር፡፡ ምን አለፋህ? የትኛዋም ሴት ምትመኘው አይነት ተንከባካቢና ከለላ አባት አገኘሁ"
ንግግሬን ገታውና ገፅታውን ቃኘሁት በፍፁም ተመስጦ እያደመጠኝ ነው፡፡ በህይወቴ ማንም ሰው እንዲህ አድምጦኝ አያውቅም፡፡ ማንም! ለዘመናት ሲርበኝ የነበረውን መደመጥ በማግኘቴ ደስ እያለኝ ማውራቴን ቀጠልኩ፡፡

"...የአሸብር መልካምነት የሆነ ወቅት ላይ አበቃ፡፡ አባቴ ያልኩት ሰው ህልሜንና ጨዋነቴን ነጠቀኝ፡፡ የደፈረኝ ቀን የሽርሙጥና መንገዴን ጠረገው፡፡.... ለሴት ልጅ በዚህ መንገድ ድንግሏን ማጣት ምን ማለት እንደሆነ አይገባህ ይሆናል፡፡ የተደፈረች ሴት ማለት በየለቱ የውርደት ሞት እንድትሞት የተፈረደባት ሴት ማለት ናት! እኔ ከተደፈርኩበት ቀን ጀምሮ በየለቱ እገረፋለሁ፡፡ በየለቱ መስቀል ላይ እቸነከራለሁ፡፡ በየለቱ እሞታለሁ፡፡ በየለቱ ወደመቃብር እወርዳለሁ ተገዶ መደፈር ማለት በየለቱ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ማለት ነው!"
አይኖቹን ጨፍኖ ራሱን ከግድግዳው ጋር አላተመ

(ክፍል ሶስት ይቀጥላል

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

"ሰውዬው" ክፍል አንድ
* * *

"በቃ አታልቅስ" አልኩት በሃዘን ተሞልቼ፡፡
በዚህ ደረጃ ለሰዎች ማዘን የምችል አይመስለኝም ነበር፡፡ ነገር ግን ከአመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሌላ ሰው ጥልቅ ሀዘን ተሰማኝ፡፡
"አታልቅስ በቃ" ደገምኩለት፡፡
"ስለእኔ አትጨነቂ" ሳግ እየተናነቀው መለሰልኝ፡፡

በጠባብ ቤት ውስጥ በተነጠፈች ትንሽ ፍራሽ ተኮራምቼ ተቀምጫለሁ፡፡ እርሱም በእኔ ትይዩ በተመሳሳይ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡
ፊቱ በሚያስፈራ ሁኔታ ገርጥቷል፡፡ አይኖቹ ወደ ውስጥ ሸሽተዋል፡፡ ከናፍሩ ከመድረቃቸው በተጨማሪ መላላጥ ጀምረዋል፡፡ ወደ ውጭ የወጣውን የደረት አጥንቶቹን የተመለከተ ማንም ቢሆን ያዝንለታል፡፡ የከሱ እጆቹ ስጋ አልባ ይመስላሉ፡፡
ስለእኔ ስነግረው ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገባ ገፅታው ምስክር ነው፡፡

"ሳምራዊት" አለኝ የአይኖቹን እንባ እየጠረገ፡፡
"ወዬ" አልኩት በልባዊ ስሜት፡፡
ለሰዎች ጥሪ በእውነተኛ ስሜት መመለስ ካቆምኩ ቆይቻለሁ፡፡ ለርሱ ግን በፍቅር ተሞልቼ "ወዬ" አልኩት፡፡ እርሱም ይህን የተረዳ ይመስል ፈገግ አለ፡፡ ሃቀኛ ፈገግታው ደስታ ያጋባል፡፡
"የሚሰማሽን ንገሪኝ" አለኝ የፊቱ ፀዳል ሳይደበዝዝ፡፡ "አይሆንም" አልኩት ከልቤ፡፡

"ምንም ነገር ልነግርህ አልፈልግም፡፡ እስካሁን በነገርኩህ ነገር ጥፋተኛ ነኝ፡፡ በጣም ራስ ወዳድ ስለሆንኩኝ ስላንተ ስሜት ሳልጨነቅ ብሶቴን ዘረገፍኩብህ:: በርግጥ የውስጤን ህመም በነገርኩህ መጠን አንዳች ቋጥኝ ከላዬ የሚነሳ ያህል ቀለል የሚለኝ ቢሆንም የኔ ስቃይ ወዳንተ እየተጋባ ከኔ በላይ አንተ እንደምትሰቃይ እያየሁ ነው፡፡... ከዚህ በኋላ ግን ስቃይህ እንዲቀጥል ስለማልፈልግ ምንም አልነግርህም" ይህን ያልኩት ከልቤ ነበር፡፡
"የኔ ተወዳጅ ስለ እኔ መጨነቁን ትተሽ ዝም ብለሽ ንገሪኝ"
"ካልክ እሺ" አልኩት ያለማመንታት፡፡ በርግጥ በውስጥ የተጠራቀመን ሸክም ማራገፍ ደስታን ይፈጥራል!

"ለአመታት የወር አበባዬ ሲመጣ እሸማቀቅ ነበር፡፡ ታውቃለህ ሞዴስ መግዣ ስለማይኖረኝ የአንሶላ ጨርቅ እንደሞዴስ እጠቀም ነበር፡፡ ይህን ያደረኩት ለአንድ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ እንጂ!.... ምናልባት ሴት ልጅ ስላልሆንክ ይህ ነገር የሚፈጥርብኝ መሸማቀቅ አይገባህ ይሆናል"
"እረዳሻለሁ፡፡ በፍፁም ልትገምቺው ከምትቺይው በላይ እረዳሻለሁ" ድምፁ ውስጥ የሆነ እውነት ያለ ይመስላል፡፡

"በመጀመሪያ ሰሞን ፔሬዴ ሲመጣ ያመኝ ነበር፡፡ ህመም ስልህ ታዲያ ዝም ብሎ ህመም አይደለም፡፡ ስቃይ ያለው ህመም! መሞትን የሚያስመኝ የሆድ ቁርጠት ነው፡፡ ሆድ ውስጥ በስለት እንደመሸነታተር ነው የሚሰማኝ፡፡ ፔሬዴ በመጣ ቁጥር ገሃነም የመጣል ያህል እታመማለሁ፡፡ ሲያመኝ ታዲያ እንደ እብድ ነው የምሆነው፡፡ ህመም ስልህ ቀላል ህመም አይደለም። አንዳንዴ ከማህፀኔ የሆነ ነገር እየተጎተተ የሚወጣ ያህል ይሰማኛል። ደግሞ የጀርባ ማቀጠሉስ? በሃይል መታመም ታውቃለህ? ለኔ በብርቱ መታመም ማለት በፔሬዴ ወቅት ያለው ህመም ነው።.... ይህ ሳያንሰኝ የአንሶላ ጨርቅ እንደ ሞዴስ እጠቀማለሁ፡፡"
አይኖቼን ወደ ገፅታው ስልክ የተናገርኩት ሃዘንን እንደፈጠረበት ተገነዘብኩኝ፡፡ ፊቱ ላይ ያነበብኩት ሃዘን 'አንድ የሚያዝንልኝ ሰው አለ ማለት ነው' ብዬ እንዳስብ ረድቶኛልና ደስ አለኝ፡፡
"ታውቃለህ" እልኩት ስሜቴ እንደሚገባው እርግጠኛ ሆኜ

"ታውቃለህ ፔሬዴ በመጣ ቁጥር መፈጠሬን እጠላ ነበር፡፡ ሴት በመሆኔ የተነሳ እድለ ቢስነት ይሰማኛልና ሴት አድርጎ የፈጠረኝን እግዚአብሔርን መራገም ይቃጣኛል፡፡ ነገር ግን ከቀናት በኋላ በአዲስ ሃይል ተሞልቼ ወደ ፊት ሊመጣ የሚችለውን ብሩህ ቀን በተስፋ አልማለሁ...."
".... አዎ ህልም ነበረኝ ትልቅ ሴት የመሆን ህልም ነበረኝ ሸርሙጣ ከመሆኔ በፊት ህልም ነበረኝ! ለማላውቀው ወንድ ቀሚሴን መግለብ ሴትነቴን መፍቀድ እግሮቼን መክፈት ከመጀመሬ በፊት ህልም ነበረኝ! ሴትነትን በገንዘብ መቸርቸር ከመጀመሬ በፊት ህልም ነበረኝ!.... ዛሬ ላይ ህልም አልባ ሸርሙጣ ብሆንም ትላንት ህልመኛና ለህልሟ የምትታር ሴት ነበርኩኝ፡፡ የጨነገፈ ህልም!.. ዛሬ ላይ ህልሜን ተነጥቄያለሁ ጨዋነቴን ተቀምቼ አለሌ ሆኛለሁ"
ጉሮሮዬን የሆነ ነገር ሲተናነቀኝና አፌ መምረር ሲጀምር ማውራት አቁሜ እንባ ባረገዙ አይኖቼ ቀና ብዬ አየሁት፡፡ እያለቀሰ ነው፡፡ ያለልክ የሚወርደውን እንባውን ስመለከት ጥፋተኝነት ተሰማኝ፡፡ የተጎሳቆለ ፊቱ በእንባው ሲታጠብ 'ባልነገርኩት' አልኩ፡፡ ነገር ግን ውስጤ 'ያጎበጠሽን ሸክም ንገሪውና ይቅለልሽ' ያለኝ ሲመስለኝ ማውራቴን ቀጠልኩ፡፡

".....ታውቃለህ ህልም ነበረኝ ትልቅ የመሆን ህልም! ደግሞም ጨዋና የተረጋጋው ልጅ ነበርኩ ከምንም በላይ መታተር ትልቁ ሃብቴ ነበር፡፡ ነገር ግን አባቴ የደፈረኝ ቀን ህልሜ ገደል ገባ ጨዋነቴ ተሻረና አለሌ ሆንኩ፡፡ በራስ መተማመኔ ከስሞ ድንጉጥነትና ፈሪነት ወረሰኝ፡፡ ታታሪነቴም በስንፍና ተተካ"
ይህን ስነግረው እያለቀስኩ አልነበረም፡፡ እርሱ ግን ተንሰቅስቆ ከማልቀሱ በላይ እጆቹና ከናፍሩ ይንቀጠቀጡ ነበር።

(አንባቢ ካለ ክፍል ኹለት ይቀጥላል


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ደራሲ ሲዲኒ ሸልደን "The other Side of me" የሚል የግለ ታሪክ መፅሐፍ አለው። እንዲህ ገናና ስም ከመገንባቱ በፊት እንዴት ያለ ፈተናን እንደተጋፈጠ እና ተስፋ ለመቁረጥ ተዳርጎ እንደነበር አብራርቷል።

በወጣትነት ዘመኑ በድብርት ህመም ይሰቃይ ነበር። ሙከራው ደጋግሞ ይከሽፍበታል፥ አሸነፍኩ ሲል ይሸነፋል፥ አገኘው ባለ ማግስት ያጣል።
አንድ ቀን ጨለማ የነገሰበት የሚመስለውን አታካች ኑሮውን አሰላሰለ። ያኔ መኖር አታክቶት ራሱን ሊያጠፋ ወሰነ።

ራሱን ለማጥፋት ከሞከረ በኋላ አባቱ የማይዘነጋ ምክር ለገሰው። "ህይወት መፅሐፍ ናት፥ እያንዳንዱ ቀን የመፅሐፉ አንድ ገፅ ነው። መፅሐፉ ተነቦ ሳያልቅ አትዝጋው" አለው።

ከዚህ በኋላ ቆም ብሎ አሰበ። "በገዛ ፈቃዴ ራሴን በመግደል የህይወቴ ገፅ እንዳይነበብ አላደርግም" አለ። ከዚህ በኋላ በመላው አለም ስሙ የናኘ ደራሲ ሆነ።

በእርግጥ ህይወታችን መፅሐፍ ብትሆን እያንዳንዱ ቀናት የመፅሐፉ ገፅ ናቸው። በመከራ መካከል ብንሆንም መፅሐፉ ተነቦ ሳያልቅ አንዘጋውም። ነገ ሌላ ቀን ነው፥ በድንግዝግዝ መሐልም ብንሆን እንኳ ሽራፊ ተስፋ አለ። እውነት መስሎ ባይታይም ጨለማው ይገፈፋል።

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ወልቂጤ ደህና አይደለችም። ባለፉት ቀናት ችግር መከሰቱ መነገር የጀመረ ቢሆንም መንግስት እንደልማዱ ጆሮ ነፍጓል።

ንፁሃን እየተቀጠፉ ነው። የመኖር መብት ያላቸው ዜጎች እንደወጡ እየቀሩ ነው።

መንግስት ለዜጎች ህይወት ደንታ የለውም።
እንዲህ የምንቀጥለው እስከመቼ ነው ?

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

የሰሜኑ ጦርነት ፍትህ ይፈልጋል። እርቅ ሙሉ የሚሆነው ፍትህ ሲሰፍን ብቻ ነው።

በአለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ጭምር ዳኝነት ሊሰጥ ይገባል።
ለዚህ ሁሉ ቀውስ ሃላፊነት የሚወስደው ማነው? የፖለቲካም ሆነ የወታደር አመራር በግልፅ ተጠያቂ መሆን አለበት።

ህወሃት ፥ ፌደራል መንግስት ፥ መገናኛ ብዙሃን ወዘተ ላዋጡት ጥፋት ተጠያቂ ሲሆኑ የተሟላ እርቅ እና ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል።

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

የቀይ ባህር ካርድ
* * *

በነ አቡነ ሳዊሮስ ጉዳይ ቤተክርስቲያን ስትታመስ ልደቱ አያሌው "ማጣላትም ማስታረቅም ጣልቃ ገብነት ነው" የሚል አርቲክል ፅፎ ነበር።

በወቅቱ መንግስት ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የቀደመ የድጋፍ መሰረቱ ስለተናደ አዲስ የድጋፍ መሰረት እየፈለገ እንዳለ እና የቤተክርስቲያን ጉዳይ ከዚህጋ እንደሚገናኝ ልደቱ ከፅሁፉ በተጨማሪ በሚዲያ በሰጣቸው ማብራሪያዎች ተናግሯል።

ቀደም ባለው ጊዜ የመንግስት ደጋፊ የነበረው "ኢትዮጵያኒስት" ካምፕ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ከመንግሥት ደጋፊነት ገሸሽ ማለቱን ተከትሎ ከኦሮሞ ብሔርተኞች ካምፕ ደጋፊ ለማሰባሰብ ጥረት መጀመሩን እና በተዋሕዶ ጉዳይም መንግስት ለነሳዊሮስ የመወገን አዝማሚያ ማሳየቱ አዲስ የድጋፍ መሰረት ፍለጋ መሆኑ ነው።

ልደቱ ያን ሰሞን አንድ ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር።

"መንግስት መጫወቻ ካርዶቹን መዞ ጨርሶል። የቀረው አንድ ካርድ ነው። አሁን ያለው አሰላለፍ የማያዋጣ መስሎ ከተሰማው ፥ ኢትዮጵያኒስት ካምፑንና የአማራ ብሔርተኞችን ለማማለል የቀይ ባህርን ወይም የወደብ ጉዳይ ማምጣቱ አይቀርም" ብሎ ነበር።

አብይና ኢሳያስ ጉሮ ወሸባዬ ሲሉ አጀንዳ ያልነበረው ወደብ ዛሬ አጀንዳ ሆኗል።

የቀይ ባህር ካርድ ተመዟል

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ስለ ፍልስጤም ደጋፊዎች
* * *

ሰሞንኛውን የእስራኤልንና የፍልስጤም ጦርነት ተከትሎ ጥቂት ያልሆኑ ኢትዮጵያን ጎራ ለይተው የቃላት ጦርነት ከፍተዋል።

በተለይ የፍልስጤም ደጋፊዎች ነገር ትንሽ ያስቃል።

ፍልስጤምን መደገፍ መብት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ እስራኤልንም መደገፍ መብት ነው። አንድ ሰው "አሏህ ፍልስጤምን ይረዳል" ብሎ የማለት ነፃነት እንዳለው ሁሉ ሌላ ሰው "እግዚአብሔር እስራኤልን ይረዳል" ብሎ የማለት ነፃነት አለው። በሚያስቅ ሁኔታ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የፍልስጤም ደጋፊዎች ይሄን እውነት ሲረሱት ማየቱ ግራ ያጋባል።
"እኔ ፍልስጤምን የመደገፍ መብት እንዳለኝ ሁሉ ሌላ ሰው እስራኤልን መደገፍ መብት አለው" ብሎ የማያስብ ሰው ምክር ሊሰጠው ይገባል።

ነገሩን ከሃይማኖት የሚያስተሳስሩ አሉ። አንዳንዱማ ፍልስጤምን አለመደገፍ እስልምና ጠልነት እንደሆነ ማሳየት ይቃጣዋል።

አንድ ሰው ፍልስጤምን በእስልምናው ምክኒያት መደገፍ መብቱ ነው። ነገር ግን የዚህን ትርጉም መረዳት አሰፈላጊ ነው። "ፍልስጤምን የማይደግፍ እስልምናን ይጠላል" የሚል ሰው በግልፅ ቃል ጦርነቱ የሃይማኖት መሆኑን እየመሰከረ ነው። እንግዲህ ጦርነቱ የሃይማኖት ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ከሱ ሃይማኖት ውጪ የሆነ ሰው የሱን ጎራ እንዲደግፍ መጠበቅ የለበትም።

አንድ ሰው 'አላቅሳ መስጂድ በሃይማኖታችን ትልቅ ቦታ አለው' ብሎ ፍልስጤምን መደገፍ እንደሚችለው ሁሉ ሌላ ሰው 'ጎሎጎታ በሃይማኖታችን ትልቅ ቦታ አለው' ብሎ እስራኤልን መደገፍ ይችላል።

አንተ የሌላ ሐገር ዜጋን ወንድሜ ነው እንደምትለው ሁሉ ሌላውም ያንተን ተመሳሳይ ማለት ይችላል።

የፍልስጤም ደጋፊዎች ላይ ለምን አተኮርኩ?

ምን አልባት የእስራኤል ደጋፊዎችም ተመሳሳይ ነገር ያደርጉ ይሆናል። ነገር ግን ማንም ተመልካች ሊታዘበው እንደሚችለው የፍልስጤም ደጋፊዎች ከእስራኤል ደጋፊዎች ይልቅ በብዛት ደጋግመው ከላይ የተጠቀሰውን ስህተት ይሰራሉ።

የግል ስሜቴን ማወቅ የሚፈልግ ካለ፥ ጦርነቱ በአጭር የሚቋጭ ቢሆን ኖሮ ማንም ቢያሸንፍ ግድ አይሰጠኝም። ነገር ግን ይህ የሚሆን ስለማይመስለኝ የጋራ ጥቅም የሚያስከብር ድርድር እንዲኖር እመኛለሁ።


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

በተማሪዎች ውድቀት ጉዳይ ተማሪዎቹን የሚወቅሱ አሉ። ተማሪዎች የራሳቸው ጥፋት ሊኖርባቸው ይችላል። ነገር ግን 97 በመቶ የሚሆን ተማሪ ወድቆ ዋናውን ጥፋት የተማሪ ማስመሰል ስህተት ነው።

መንግስት ለተማሪዎች የመማሪያ መፅሐፍ እያቀረበ አይደለም።
የማስተማር ሂደቱ ላይ ምንም አይነት ማሻሻያ ሳይደረግ የፈተና አሰጣጡ ላይ ለውጥ ተደርጓል። የመንግስት ዋና ሚና ማስተማር እንጂ ፈተናን ጥብቅ ማድረግ አይደለም። ፈተና ከማስተማር በኋላ የሚመጣ ነው።

በርካታ ተማሪዎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሆነው ነው የተማሩት። በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች በግጭት ሰበብ ተማሪዎች በአግባቡ ሊማሩ አልቻሉም። ግጭት አስወግዶ ፥ ሰላም ማስፈን የመንግስት ሚና ነው።

በየክፍላቸው በደረጃ የሚወጡ በርካታ ተማሪዎች ሲወድቁ ሲስተሙን በመፈተን ፈንታ 'ተማሪዎች ሰነፍ ስለሆኑ ወደቁ' ማለት አጓጉል ስላቅ ነው።

መንግስት ለትምህርት እና ለሙህራን ተገቢውን ክብር እንደማይሰጥ ደጋግሞ አሳይቷል። በጦርነት የተነሳ የፋይናንስ ችግር አለበት። የትምህርት በጀት ተቀንሶ ለጦር እንዲውል ስለመደረጉ ፥ በተማሪዎች ፈንታ ለውትድርና ትኩረት ስለመሰጠቱ ጥርጣሬ ቢኖረን እንደ ጥፋት ሊቆጠር አይገባም።

ከተወሰኑ አመታት በፊት በኢትዮጵያ በየአመቱ 2 ሚሊየን ስራ ፈላጊ ቢፈጠርም ስራ የሚፈጠረው ለ 1 ሚሊዮን ሰው ብቻ ነው። ይህ ማለት በየአመቱ 1 ሚሊየን ስራ አጥ ይመረታል።
ይህ ችግር ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ መምጣቱ እውን ነው።

በዚህ ሁኔታ ከዩኒቨርስቲ ለሚመረቁ ተማሪዎች ስራ መስጠት የተሳነው መንግስት ፥ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ ሳይገቡ በፊት እየጣላቸው እንደሆነ ብንረዳ አይፈረድብንም።

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

"የአብርሃም ስምምነት፥ ሰላም ለእስራኤል ሰላም ለአረቡ አለም"
* * *

መካከለኛው ምስራቅ ደም መፋሰስን የለመደ፥ ሺ ዘመን የተሻገረ የውጊያ ታሪክ ያለው ፥ ለብያኔ በሚያስቸግር የታሪክ እና ፖለቲካ ትብታብ የተተበተበ ነው።
በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል እንኳ በየዘመኑ የሚያገረሽ ግጭት ይደረጋል። ሰላም ወረደ በተባለ ማግስት ተፋላሚዎቹ ጦር ይሰብቃሉ።

"የአብረሃም ስምምነት" በእስራኤል እና በበርካታ የአረብ ግዛቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስተካከል በማቀድ የተደረገ ውል ነው።
ስምምነቱ 'የአብረሃም ውል' የተባለው የአይሁድ እና የአረቦች የጋራ ቅድመ አያት ከሆነው አብረሃም ጋር በማስተሳሰር የወንድማማችነት መገለጫ እንዲሆን ነው።

ዳራ እና አውድ

እስራኤል በ1948 "ነፃነቴን አግኝቻለሁ፥ ከዛሬ ጀምሮ ሉአላዊ ሐገር ነኝ" ብትልም የአረቡ አለም መንግስታት ለእስራኤል እውቅና ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ።
ይባስ ብሎ በአረብ እና በእስራኤል መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነቶች በተከታታይ ተካሄዱ።

ስመ ገናናውን 'የስድስት ቀን ጦርነት' ጨምሮ የተለያዩ ደም መፋሰሶች ከተደረጉ በኋላ ግብፅ እና እስራኤል የካምፕ ዴቭድ ስምምነት የተሰኘ የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ከፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅች (PLO)ጋር እስራኤል በ1979 የሰላም ስምምነትን ፈረመች።

የሰላም ስምምነት ውሎች የጦርነትን ድባብ ያስወገዱ አልነበሩም። የተዳፈነው ረመጥ እየተቀሰቀሰ በተካታታይ ጦር መሳበቅ ፥ ቃታ መሳሳብ ፥ ደም መፋሰስ ቀጠለ።
በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ወቅት እየጠበቀ የሚያገረሸው ውጊያ ዘላቂ መፍትሄ ባይበጅለትም በባህረ ሰላጤው አረብ ሀገራት እና በእስራኤል መካከል የጋራ ጥቅም ዳበረ፥ አይሁዶችና አረቦች እንዲተባበሩ የሚገፋፋ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ጎለበተ።

"የአብርሃም ስምምነት" እስራኤል ከአረብ ሀገራት ጋር የነበራትን ግንኙነት ወደ አደባባይ ያወጣ፥ የአረብ-እስራኤልን ግጭት መልክን የለወጠ ነው።

የአብርሃም ስምምነት መግለጫ ፅሁፍ እንደሚከተለው ይነበባል

"እኛ፥ በመካከለኛው ምስራቅ እና በመላው አለም በጋራ መግባባት እና አብሮ መኖር ላይ የተመሰረተ ሰላምን የመጠበቅ እና የማጠናከር አስፈላጊነትን እንረዳለን። የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ ለሰው ልጅ ክብር እና ነፃነት መከበር ያለውን ጠቀሜታ እንገነዘባለን"

"በሦስቱ የአብርሃም ሃይማኖቶች እና በሁሉም የሰው ዘር መካከል የሰላም ባህልን ለማራመድ የሃይማኖቶች እና የባህላዊ ውይይቶችን ለማስፋፋት ጥረቶችን እናበረታታለን"

"ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የተሻለው መንገድ ትብብር እና ውይይት በመሆኑ በቀጠናው ወዳጃዊ ግንኙነት ማዳበር በመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በአለም ላይ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል ብለን እናምናለን"

"አለማችን ፥ የሰው ዘር ሁሉ፥ ሃይማኖት ወይም ጎሳ ሳይለያይ ሁሉም በክብር እና በተስፋ የሚደሰትበት እንድትሆን ለማድረግ መቻቻል እና አክብሮትን እንዲሰፍን እንፈልጋለን"

"የሰው ልጅን ለበጎ አላማ ለማነሳሳት፥ የሰውን አቅም ከፍ ለማድረግ እና ሀገራትን ለማቀራረብ ሲባል ሳይንስ፥ ኪነጥበብ፥ መድሃኒት እና ንግድን እንደግፋለን"

"ለሁለም ልጆች የተሻለ የወደፊት እድል ፈንታ ለመስጠት በማሰብ ጽንፈኝነትን እና ግጭትን ለማስቆም እንፈልጋለን"
"ራዕያችን በመካከለኛው ምስራቅ እና በአለም ዙሪያ ሁሉ የሰላም፥ የደህንነት እና የብልጽግና ነው"

"በአብርሃም ስምምነት መርሆች መሰረት በእስራኤል እና በአካባቢው ባሉ ጎረቤቶቿ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት የተደረገውን እናበረታታለን"
"የጋራ ፍላጎቶች ላይ መሰረት በማድረግ ወዳጃዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር እና ለማስፋት እንጥራለን"

የአብረሃም ስምምነት ይዘት ፀረ ግጭት ቢሆንም መካከለኛው ምስራቅ ግን ከውጊያ ነፃ ሆኖ አያውቅም። ዛሬም እንደ ቀድሞው ዘመን ሁሉ የጦርነት እሳት ተለኩሷል

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ልደቱ አያሌው፥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውድቀት ማሳያ !
* * *

የኢትዮጵያ ፖለቲካን ብልሽት ለማወቅ አይነተኛው ሰው ልደቱ አያሌው ነው።

ማንም ሰው የልደቱን ሃሳብ የመቀበል ግዴታ ባይኖርበትም እሱ ሃሳብ ያለው ፖለቲከኛ መሆኑ አይካድም።
አማራጭ ሕገመንግሥት ማዘጋጀትን ጨምሮ በዝርዝር የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አማራጭ ሃሳብ አቅርቧል፥ ተሟግቷል። 'ሃሳቦቹ የግድ አሸናፊ ሊሆኑ ይገባል' የሚል ክርክር መግጠም አግባብ ባይሆንም የሱን ሃሳብ ውድቅ የሚያደርግ አማራጭ ሃሳብ መቅረብ ነበረት።

3 አስርት አመታት በተሻገረ የፖለቲካ ህይወቱ ለሰነዘራቸው ሃሳቦች ፥ ላራመዳቸው አቋሞች ፥ ለተከተለው ርዕዮት ተቃራኒ የሆነ መሟገቻ በማቅረብ ፈንታ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶበታል። ሃሳብን በሃሳብ ከመሞገት ይልቅ አሉባልታ አማራጭ ሆኗል።

ሃሳብ የሰነዘሩ ሰዎች ላይ የአሉባልታ ዘመቻ መክፈት የፖለቲካችን ውድቀት ማሳያ አይደለም?

በፃፋቸው አምስት መፅሐፍትና በርካታ አርቲክሎች ፥ በሚሰጣቸው ቃለመጠይቆች ሁሉ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ሲያስተዋውቅ ቢከርምም ፀሐዩ መንግስታችን 'ልደቱ አሸባሪ ነው' ብሎታል።
ፖለቲካችን ደም የተጣባው ነው። ከሰላም ይልቅ አመፅ ምሱ ነው። ከሰላም ፖለቲካ አራማጁ ልደቱ አንፃር ፖለቲካችንን ብንገመግም ያለጥርጥር የፖለቲካችንን ብልሸት ጎልቶ ይታያል።

በመርህ ጉዳይ አለመፎረሹን ደጋግሞ አሳይቷል። በኦሮሚያ ፥ በትግራይ ፥ በአማራ ፥ በቤንሻኔገል ወዘተ ያሉ ጦርነቶችን በተመለከተ ከሚታመንለት እሴት የመነጨ መርህ ተከል አቋም ሲያራምድ ከርሟል።
ፖለቲካችን መርህ የለሽ ነው። ፖለቲከኞቻን ጠዋት ያራመዱት አቋምና ከሰኣት የሚያራምዱት አቋም ደጋግሞ ቢላተምም ግድ አይሰጣቸው።
በግልፅ መርህ የሚታወቀውን ልደቱን ያስተዋለ መርህ አልባ የሆነውን ፖለቲካችንን የውድቀት ልክ ይረዳል።

ኤሊት እና ህዝብን ደበላልቆ አይመለከትም። በሊህቃን ጥፋት የህዝብን ጥያቄ አይክድም። በኦሮሞ ኤሊት የተነሳ የኦሮሞን ጥያቄ አያድበሰብስም ፥ በአማራ ሊህቃን መነሻ የአማራን ህዝብ ሐቅ አይክድም ፥ በትግራይ ፖለቲከኞች ሰበብ የትግራይን ህዝብ እውነት አይሸፍንም። ግልፅ በሆነ ሁኔታ ህዝብና ሊህቅን ይለያል።

ፖለቲካችን ከሱ ተቃራኒ በሆኑ ሰዎች መሞላቱን ስናስብ የፖለቲካችን ብልሽት ልክ ያሳስበናል

ህዝበኛ አይደለም። ለሰው ጆሮ ተስማሚ የሆነ ንግግር በማድረግ ጭብጨባን ከመቃረም ይልቅ የሚያምንበትን አቋም መራራ ቢሆን እንኳ በድፍረት ያራምዳል።
በተቃራኒው አየሩን የተቆጣጠሩ ፖለቲከኞቻችን ውግዘት እና ነቀፋን በመፍራት ህዝብ የሚወደውን ብቻ ለማውራት ሲራኮቱ ስናይ በእርግጥ የፖለቲካችን ብልሽት ልክ ይታየናል።

ከሐሳብ ተቃራኒዎቻቸው ጋር መወያየትን የማይደፍሩ ፥ ለቃለመጠይቅ ሚዲያ የሚመርጡ ፖለቲከኞች በሞሉበት ሐገር ከማንም ጋር ለመወያየት መድፈር በሁሉም ጫፍ በቆሙ ሚዲያዎች ለመሟገት መፍቀድ የልደቱ ልዩ ብራንድ ነው።

ፖለቲካችን መርህ አልባ ፥ ህዝበኝነት የተጣባው ፥ አሉባልታ የነገሰበት ነው።
ፖለቲካችን ልደቱን እና በቁጥር ጥቂት የሆኑ የርሱ ቢጤዎችን ከማክበር ይልቅ የሚገፈትር መሆኑ የሚነግረን ነገር የሐገራችንን ፖለቲካ ውድቀት መጠን ነው

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

በአንድ እንቅፋት ሦስቴ ፥ ክፍል ሁለት
* * *

"ጥያቄ ስጠይቅህ የማትመልስልኝ ለምንድነው?"
"አትበሳጪ"
"አትሳቅ... ከልቤ ነው የምጠይቅህ እኮ"
በዝምታ ወደ ከንፈሯ ተንደረደርኩ፥ አፀፋውን መለሰች። እጆቼን ከወገባ በታች አወረድኩ። የሸሚዜን ቁልፎች ፈታች...
............
............
.............

"መተዋወቅ አለብን" አለችኝ ከወሲብ በኋላ
"ስንት ጊዜ እንተዋወቃለን?"
"በእውነተኛ ስማችን እንተዋወቅ"
"ጥሩ ሾፍሬሻለሁ ማለት ነው"ተሽኮረመመች።....
ሴተኛ አዳሪ መሽኮርመም የማትችል የሚመስለኝ ለምንድነው? መሽከርመሟ እንደ ልዩ ተአምር የሚያስደንቀኝ በምን ምክንያት ይሆን?

"ጥሩ ነበርኩ አይደል?"
በሃፍረት ጀርባ ስትሰጠኝ ሆን ብዬ ድምፄን ከፍ አድርጌ ሳቅኩ።
"ተወው በቃ" አንሶላው ስር ገባች።
"ምኑን ልተወው?"
"መተዋወቁን ነዋ"
"ስትናደጂም ታሻፍጃለሽ"
"ሂዛ"
"ያቤፅ እባላለሁ"
"እየሩሳሌም እባላለሁ። እየሩሳሌም አስግዶም"
"የአስግዶም ልጅ ሆነሻል ለካ" ሳቅኩባት
"የአስግዶም በርሔ ልጅ ነኝ" ከፍ ባለ ድምፅ ሳቀች
"ወቅታዊ ጉዳይ ትኩረትሽን የሳበበት ምክንያት አሁን ተገለጠልኝ"

"ወንድሜ ዘምቷል" አለችኝ
"በሰሜኑ ጦርነት?"
"አዎን!"

ተበሳጨሁ። ምናልባት ከፌደራል መንግስት ጎን የተሰለፈው ወንድሜ ከህወሓት ጋር የተሰለፈውን ወንድሟን ይገድል ይሆናል። አሊያም የእርሷ ወንድም የእኔን ወንድም ያጠፋዋል።..... ምንድነው እየሆነ ያለው?

"በጣም በሽቄበታለሁ። በፍፁም መዝመት አልነበረበትም።... ገና በ 19 አመቱ ለመግደል ወይንም ለመሞት መሰለፍ አልነበረበትም። እኔ ስለማንም የፖለቲካ አላማ ግድ አይሰጠኝም። ብትፈልግ ታዘበኝ ከሃገሬም ከብሔሬም ወንድሜ ይበልጥብኛል"
"እረዳሻለሁ"

"አባቴ የህወሓት ታጋይ ነበር። ያኔ ወያኔዎች ደርግን ለመጣል በረሃ ሲወርዱ ተከትሏቸው በረሃ ከወረዱ ጎረምሶች መካከል ነበረበት።... የደርግ አገዛዝ ከተገረሰሰ በኋላ በውትድርናው ገፍቶ እስከ ኮሎኔልነት ደርሷል።.... ያረፈው የዛሬ 11 አመት ነው"

ምን ማውራት እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ ሳለ ንግግሯን ቀጠለች

"በጣም በሚያስቅ ኹኔታ የኤርትራ ወታደር የሆነ ዘመድ አለኝ። ያውም የእናቴ ወንድም ልጅ! የሚገርምህ በባድመ ጦርነት ነው የሞተው። በባድመ ጦርነት እናቴ ከኹለት ወገን የእኔ የምትለው ሰው ነበራት። አባቴ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር ጦርነት ውስጥ ገብቷል። የወንድሟ ልጅም በኤርትራ ወገን ተሰልፏል። አደይ በሁለቱም ወገን ያለ ኪሳራ ይጎዳታል። በኹለቱም በኩል ትታመማለች"

"እኔና አንቺ ተቃቅፈን በተኛንባቸው ምሽቶች የእኔና ያንቺ ወንድሞች ተቃራኒ ሆነው ይፋለማሉ"
ማን ላይ እየተቆጣሁ እንደሆነ ባላውቅም በቁጣ ነው የተናገርኩት።

"ፖለቲካ ሽርሙጥና ነው። ሽርሙጥና!"
የአልጋውን ራስጌ ተደግፋ ጡቷን በአንሶላ ሸፍና ሲጋራ ለኮሰች

"እስከመች? በየጊዜው ተመሳሳይ አዙሪት? በየአጋጣሚው የቅርባችንን ሰዎች እየተነጠቅን እንቀጥል?" ያነቃት ሳግ ንግግሯን ገታው

የማንም ደንቆሮ የማይገባውን ስልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ በሚያፈልቀው ሃሳብ የተነሳ ተያይዘን የምንወድቀው እስከመች ነው? መጥገብ ያልፈጠረባቸው አግበስባሾች ላልተገራ ፍላጎታቸው መስዋዕት እያደረጉን መቀጠላችን ልክነት የሚኖረው በምን አግባብ ነው?
አእምሯቸውን እብሪት የጋረደባቸው እብዶች በተሳሳቱ ቁጥር የጥፋታቸው መቀጣጫ እንሆናለን። አለአዋቂ በመሆናቸው የተነሳ የከበደብን ቀንበር ሳያንሰን የጎበጠ ትኬሻችን ላይ ጅራፍ ይጨመርብናል።
ጥያቄያችን 'የጎበጠ ጫንቃችን እንዲቀና አድርጉልን' የሚል አይደለም። ልመናችን 'የተጫነብን ቀንበር ከብዶናልና ሌላ አትጨምሩብን' የሚል ነው። ለህመማችን ፈውስ ፈልጉልን አንልም። ያልሻረ ቁስላችን ላይ እንጨት እየሰደዳችሁ አታመርቅዙብን እንጂ!
ባሮች ነን። በእርግጥ እኛ ባሮቻቸው ነን። ትፋታችንን እንድንልሰው ስንገደድ እንኳን 'አይሆንም' የምንልበት አቅም የሌለን ባሮች ነን።... መሻታችን የሚያርፍብን የእርግጫ ብዛት እንዲቀንስልን ነው። መግረፊያ ጅራፉ እሾኻማ አይሁንብን የሚል የአቅመ ቢስ ምኞት ነው ያለን።... መጥገብን አልተመኘንም። ይልቅ ከገዛ እጃችን ከተነጠቀው ላይ ርሃባችንን የሚያስታግስልን ያህል እንዲወረወርልን ፈለግን እንጂ! የኛው ከሆነው ላይ ነብሳችንን የምታቆየውን እጅግ ጥቂቱን ብቻ ፈለግን!
የሚገባን እጅግ ብዙ ነበር.... እጅግ ብዙ ሲገባን እጅግ ጥቂቱን እንኳን ተከለከልን። የኛው የሆነውን ከነጠቁን ላይ ለመለመን ተገደድን። ክብራችን ተገፎ ከውሻ በታች ሊያደርጉን ለወደዱቱ ሁሉ ጎዶሏችን ይሞላልን ዘንድ ከእግራቸው በታች ሆነን ተረገጥንላቸው። 'ነገ መልካም ይሆናል' በሚል የማይጨበጥ ተስፋ ራሳችንን ሸነግልን።.... ያልታደልን!

"እያለቀስክ ነው?"
"ከማልቀስ ውጭ ምን ማድረግ እችላለሁ?"
"አታልቅስ" እርሷም እያለቀሰች ነበር።... እየተላቀስን ተቃቀፍን።...
ያልተነጠቅነው ሃብታችን እንባ ብቻ ነው!
እስከዛሬ ድረስ ብዙ ተነጥቄያለሁ። ለአገሬ ያለኝን ፍቅር እና ክብር እንኳን ተነጥቄያለሁ። ሰብኣዊ ስሜቶቼን ተቀምቻለሁ።...

ከፖለቲካ ተዋናዮቻችን መካከል ብዙሃኑ ባሪያ ፈንጋይ ናቸው። ፈርጣማ ሆነን ብንገኝ እንኳን ለባሪያ አሳዳሪዎች ብንሸጥ የተሻለ ዋጋ የምናወጣላቸው አድርገው ከማሰብ አይመለሱም።... በእኛና በነርሱ መካከል ያለው ግኑኝነት የሎሌ እና ጌታ እንዲሆን ያለ እረፍት ይታትራሉ። ይህን እንዳናውቅባቸው በረጅም ገመድ ያስሩናል።
ሆዳም ነጋዴዎች ናቸው። ብሔራችንን ይነግዱበታል፥ በሃይማኖታችን ትርፍ ያጋብሳሉ፥ በቁስላችን ባለጠጎች ይሆናሉ፥ በረሃባችን ይጠግባሉ። ሸቀጦቻቸው ያደርጉናል!
አላምናቸውም! ማናቸውንም አላምንም!
እምነት አልባ አድርገውኛል። የእምነት እሴታችንን በጭካኔ ንደውታል። መጎዳቴ ያስለቀሳቸውን እንኳን ነገ ጦር ሊሰብቁብኝ እንደሚችሉ እያሰብኩ እፈራለሁ።...... እምነትና ተስፋን ነጥቀውናል! ክፉዎች!

"ሆደ ባሻ አትሁን እንጂ"
"ከብሶት በቀር ምን ማድረግ እንችላለን?"
"መደሰት እንችላለን። ነገ ጠዋት በፖለቲካ አመፅ እንሞት ይሆናል፥ ወይንም ተባራሪ ጥይት ይበላናል፥አሊያም መንጃ ፈቃዱን በገንዘብ የገዛ ሹፌር ገጭቶ ይገድለናል፥ ከዚህ ከተረፍን በሰካራሞች አንባጓሮ እንሞታለን፥ ወይንም በጎሳ ግጭት ሰበብ እናሸልባለን፥ ይህ ቢያልፈን ግድ የለሽ ሂኪም የተሳሳተ የህክምና መርፌ ወግቶን እስከወዲያኛው እናንቀላፋለን፥ ምናልባት ደግሞ በኑሯችን ተማረን ራሳችንን እንገድላለን።.... ዙሪያችን በሞት የተከበበ ነው"

"በእርግጥ በሞት ተከበናል! የሞት መልአክ ሰይፉን ከሰገባው መዞ ያንዣብበናል፥ ምክኒያቱም እኛ ኢትዮጵያን ነን። ብዙ የመሞቻ ምክኒያት እና ጥቂት እድሜ ማራዘሚያ ሰበብ ያለን ነን!"

"እስክንሞት ድረስ አለማችንን መቅጨት አለብን"

"በእርግጥ ደስታን ማጣጣም አለብን!"

ወደ ከንፈሬ መጣች፥ ወደ ከንፈሯ አቀናሁ፥ እጆቼን ወደ ጡቶቿ ሰደድሁ፥ በእግሮቿ ጭምር አቀፈችኝ፥ ከንፈሯን ሳምኩ፥ ከንፈሬን ጎረሰችው።

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

የገዳዩ ኑዛዜ
* * *

በዘመነ-ደርግ ሕዳር 14 ቀን 1967 አ.ም በተለምዶ 60ዎቹ የሚባሉት እና በአንድ ጀንበር የተገደሉቱ ሰዎች ነገር ለዘመናት ሲያነጋግር ከርሟል።

ደርግ ያለ በቂ ምክኒያት ሰዎችን ከመረሸኑ በፊት ስለሰዎቹ እጣ ፈንታ ስሜት የተጫነው ውይይት ያደረገ ሲሆን መገደላቸውን ብርሃኑ ባየህ ብቻ መቃወሙን ፍቅረስላሴ ወግደረስ ፅፏል። ብርሃኑ ባየህ "ግድ የላችሁም ሕጋዊ መንገድ እንጓዝ፥ ፍርድ ቤት ይወስን፥ ሕግ ነፃ ካደረገ ነፃ ይሆኑ፥ ከቀጣቸው ይቀጡ። እኛ ግን ስልጣናችንን ተጠቅመን መወሰን የለብንም" ብሎ የነበረ ቢሆንም ሰሚ አላገኘም። ሰዎቹ ተረሸኑ።

ጎህ መፅሔት ቆየት ባለ እትሙ ያልተለመደ ጉዳይ ስለሟቾቹ አስነብቦ ነበር። አስር አለቃ ደሳለኝ 'ሰዎቹን የገደልኩት እኔ ነኝ' ካለ በኋላ ዝርዝሩን አብራርቷል።
ጓድ መንግስቱ "ልዩ ተልእኮ አለ፥ ይህን በአግባቡ ከፈፀማችሁ ሽልማት አላችሁ ካለን በኋላ እኔና ጓደኛዬ ለተልእኮ ተሰማራን" ብሏል።

በዛ ፅሁፍ አንዳንድ አስገራሚ መረጃዎች ተካተዋል።
እስከ አሁን የሚታወቀው የሟቾች ቁጥር 59 እንደሆነ እና 60ኛው ጀነራል አማን አምዶም እንደሆነ ቢሆንም አስር አለቃው "የገደልናቸው 83 ሰዎች ነበሩ" ብሏል።

የመጀመሪያ ተረሻኝ የነበሩት አክሊሉ ሀብተ ወልድ እና የስጋ ዘመዳቸው የሆኑ አዛውንት ሲሆኑ ወደ መግደያ ቦታው ሲደርሱ አዛውንቱ መሳሪያውን ተመልክተው ደነገጡ፥ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው መጮህ ጀመሩ። ሊገደሉ እንደሆነ ሲገባቸው "ተፈታችኋል ብላችሁ የዋሻችሁን ለዚህ ነበር? ያለ ፍርድ ልትጨርሱን ነው?" እያሉ ጮኹ።

ኢትዮጵያን በተለያየ ቦታ ያገለገሉት እና ጠቅላይ ሚኒስቴር እስከመሆን ደርሰው የነበሩት አክሊሉ ሃብተወልድ ግን "ሐገሬን ላገለገልኩበት የሚገባኝ ይኽ ነበር? እድሜዬን ሙሉ ኢትዮጵያን ሳገለግል ቆይቼ ክፍያዬ ሞት ሆነ?" አሉ።
ሁለቱም ተገደሉ።

ከተገዳዮች መካከል አንዱ የሆኑት ጀነራል አብይ አበበ ተራቸው ሲደርስ ተረጋግተው "ልጆቼ ሳታሰቃዩ ጨርሱኝ። አደራ ጣራችንን እንዳታበዙት ፥ እንዳታሰቃዩኝ። ቶሎ ግደሉኝ" ብለው ገዳዮቹን ተማፀኑ።


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ጆሴፍ ጎብልስ፥ የገዛ ሚስትና ልጆቹን የገደለው የፕሮፓጋንዳ ንጉስ
* * *

እርሱ ያለጥርጥር የፕሮፕጋንዳ ንጉሰ ነው። ሃሰትን እውነት አስመስሎ ማቅረብን ያውቅበታል ፥ ጥቂት እውነትን በውሸት ለውሶ ለህዝብ በመጋት ተክኗል።
ጆሴፍ ጎብልስ ይባላል። በፈረንጆች የዘመን ቀመር ጥቅምት 29 ቀን 1897 ከእናቱ ማህፀን ወደ ፕላኔታችን ተቀላቀለ።

ሂትለር በመንበር ሳለ የናዚ መንግስት ዋናኛ አንደበት ነበር። በተካነው የፕሮፓጋንዳ ሙያ የናዚን መልእክት ለህዝብ ያስላልፋል፥ ህዝቡን ከጨካኙ መሪ ጎን ያሰልፋል።
ዋና ሚናው ለናዚ በጎ ምስል መስጠት ፥ የጀርመንን ብሔርተኝነትን ማጋጋል ፥ ሂትለርን በስሜት የሚከተል መንጋ እንዲፈጠር ማድረግ ነው።

የናዚ አቃጣይ ፀሐይ ጠልቃ የሽንፋት ፅዋን መከናነባቸውን ተከትሎ አዶልፍ ሂትለር ራሱን ሲያጠፋ ፕሮፖጋንዲስቱ ጎብልስ የጀርመን ቻንስለር ሆኖ ነበር። የቻንስለርነት እድሜው ግን 24 ሰአት ብቻ ሆነ

ንግግር አዋቂነቱን ለሰይጣናዊ አላማ ያዋለው ፥ ብርቱ አንደበቱን ህዝብ ለማሳሳት የተጠቀመው የፕሮፖጋንዳው ንጉስ ጎብልስ በጎርጎሪያሳዊያኑ አቆጣጠር 1922 ወደ ዩኒቨርሲቲ ዘልቆ በፊሎሎጂ ዶክትሬት አግኝቷል።
በ1920ዎቹ ደግሞ ልብ ወለድ በመፃፍ ስነ-ፅሑፋዊ መሰጠቱን አሳይቷል።

በፖለቲካ ዘመኑ አይሁዳውያንን የሚያሳድድ ፀረ ሰማዊ ቢሆንም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ምስጉን አይሁዳዊ መምህራን ነበሩት። በአንድ ሰሞን ደግሞ ከፊል አይሁዳዊት ከሆነች እንስት ጋር በፍቅር ወድቆ ለመተጫጨት ደርሶ ነበር።

ጎብልስ የናዚ አንደበት ከሆነ በኋላ የንግግር ብቃቱን በመጠቀም በርካቶች በሂትለር ዙሪያ እንዲሰባሰቡ አድርጓል። ክፉትን ቅዱስ አስመስሎ ከማቅረቡ በዘለለ ጥቂት ያልሆኑ ሰዎችን በፕሮፖጋንዳ ብቃቱ አእምሯቸውን በመስለብ ለጥፋት አሰልፏቸዋል።

ፕሬስን፥ ሬዲዮን ፥ ቲያትርን ፥ ፊልምን፥ ሥነ ጽሑፍን፥ ሙዚቃን ወዘተ በቁጥጥሩ በማስገባት ለቅስቀሳ አላማ ተጠቅሟቸዋል።

ጎብልስ ለህዝቡ በድል አድራጊነት ስሜት "የጽንፈኛ የአይሁዳዊያን ምሁርነት ዘመን አብቅቷል" እያለ ሲቀሰቅስ አይሁዳዊያንን ለመጨፍጨፍ መደላድል እያበጃ ነበር። 'አይሁዳዊያን ማንነታቸውን ጫኑብን' የሚል የተጠና ፕሮፖጋንዳ በማስረፅ ህዝቡ አይሁዶችን ለመቅጣት እንድነሳሳ ቀስቅሷል።

የሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ጀርመን ድል እየከዳት እንኳ ጎብልስ የፕሮፖጋንዳ ጥበቡን በመጠቀም ጀርመናዊን በውጊያ እንዲቆዩ አድርጓል።

ከደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የናዚ ፀሐይ ጠለቀች። ጨካኙ የሂትለር ጦር ሽንፈትን ተከናነበ።
በአስፈሪ ጭካኔ ብዙሃንን ወደ ሞት ሲሰድ የነበረው አዶልፍ ሂትለር መሸነፉን ሲያውቅ በሚያዝያ 30፥ 1945 እራሱን ገደለ። ከአለቃው ሞት በኋላ አፈቀላጤው የጀርመን ቻንስለር ሆኖ ነበር። ስልጣኑ ግን የአንድ ቀን ብቻ ሆነ።

ቻንስለር በሆነ ማግስት ባለቤቱን ማክዳን እና ስድስት ልጆቹን ሰበሰበ። ቀጥሎ ሲያናይድ የተባለ መርዛማ ኬሚካል በመጠቀም ከአብራኩ የተወለዱትን ስድስት ልጆች እና የትዳር አጣማሪ የሆነችውን ሚስቱን ገደለ።

አዎ፥ የገዛ ሚስቱን እና ልጆቹን ገደሏቸው እርሱም ራሱን አጠፋ።

@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

ሌንጮ
* * *

''ሌንጮ የምወደው ደንበኛዬ ነበር ብዬህ አይደል?"
"ብለሽኛል"
"በህይወቴ የማልረሳውን ምሽት ሰጥቶኛል"
"ገባኝ"
"አልገባህም"
"ገብቶኛል!"
"ስለ ወሲባዊ እርካታ አይደለም!"
"ታዲያ ምንድነው?"
"ክብር... ርህራሄ.... መከበር.... ዋጋ ማግኘት"
"አስረጂኝ"

"አንድ ምሽት አዳር ፈልጎ መጣ። በወር ወይም በሁለት ወር አንዴ እየመጣ ያድራል። በጣም ጠንቃቃ እና ለሰው ክብር ያለው ሰው ስለሆነ አብሬው ማደር ደስ ይለኛል። ለሰዎች ስሜት ይጠነቀቃል፥ የሌሎችን ፍላጎት ያከብራል፥ አዳር ብሎ ቢመጣም ከሁለት ዙር በላይ አይሄድም። ሁለቴ ካደረገ በኋላ 'ደህና እደሪ' ይለኝና በጀርባው ተንጋሎ ኮርኒሱ ላይ እያፈጠጠ ጣቱን ይፈትጋል"

"ለአዳር ከፍሎ ሁለት ዙር አያዋጣም" የማብሸቅ አይነት ሳቅኩባት

"ከብዛት ጥራት ሲባል አልሰማህም"
"በጥራት ይሾፍራል እያልሽኝ ነው?"
"አብሬው ባደርኩ ቁጥር ያስጨርሰኛል። ጎበዝ ነው" የሃፍረት ሳቀች።
"ለዚህ ነው የምትወጂው?" ከቅናት ስሜት ጋር ትግል ገጠምኩ
"አይደለም"
"ለምንድነው ታዲያ?"
"አንድ ቀን ለአዳር መጣና ከገባን በኋላ ሃሳቡን ቀየረ"
"ለምን ቀየረ?"
"ያን ምሽት የጥርስ ህመሜ ተነስቶብኝ ነበር። ሃይለኛ የጥርስ ህመም አለብኝ፥ ሲነሳብኝ ለሳምንት እታመማለሁ።... ለሁለት ቀናት ቤቴ ካሳለፍኩኝ በኋላ ነው ወደ ስራዬ የተመለስኩት።... ሌንጮ ሁለቱን ቀናት መጥቶ እንዳጣኝ እና እኔን ከመልመዱ የተነሳ ከሌላ ሴት ጋር ማደር አለመፈለጉን ነገረኝና ደስ አለኝ። ኩራት ተሰማኝ። ምንም እንኳን ሴተኛ አዳሪ ብሆንም ሰዋዊ ስሜቶች አሉኝ። የመፈለግ ስሜት ልቤን ያሞቀዋል። በገዛ ገንዘቡ የሚተኛኝ የወሲብ አገልጋዩ ብሆንም እኔ በሌለሁበት ጊዜ ከሌላ ሴት ጋር አለመውጣቱን ሲነግረኝ ለደንበኝነታችን ያሳየው መታመን አኮራኝ። ሴተኛ አዳሪዎች መታመን የማይገባን ይመስላችኋል አይደል? ሌንጮ ግን እንደሌሎቻችሁ ደደብ አይደለም"

እንደወራጅ ውሃ ሳይደነቃቀፍ ሲፈስ የነበረ ንግግሯ ድንገት ተገታና ዝም አለች። በሞቀ ስሜት ማብራራቷ ተቋርጦ ድንገተኛ ትካዜ መታት። ስሜቷ ደፈረሰ።

"ሊሊ"
"ወይ" ድምጿ ሻክሯል
"ሊሊዬ ይቅርታ"
"ባይሆን የሆነውን ልንገርህ"
"እያለቀስሽ እኮ ነው"
"ናፈቀኛ"
ወንበሬን ወደርሷ አስጠጋሁትና አቀፍኳት
"ይቅርታ" ቅድም ሲሰማኝ የነበረው ቅናት በሃዘን ተተካ
"ልንገርህማ"

የሚበቃትን ያህል ካለቀሰች በኋላ ከእቅፌ ወጥታ ፊቷን በእጆቿ አፀዳዳች

"ለመጨረሻ ቀን አብረን ስናድር ጥርሴን እያመመኝ እንደሆነ ሲያውቅ አዘነልኝ። ከሱ በፊት ከሁለት ደንበኞቼ ጋር ሾርት ወጥተን ነበር። ሁለቱም እያመመኝ እንደሆነ አውቀዋል ግን ምንም አልመሰላቸውም። እንዲታዘንልኝ ስለፈለግኩ፥ 'እኔን ይመመኝ' እንዲሉኝ ስለተመኘው፥ ለሁሉም ህመሜን ተናግሬያለሁ። ማንም ግን አላዘነልኝም። ይጋልቡኝ ችግር የለውም፥ ከፍለውኛላ! እሱን አልከለከልኩም። 'እያመመኝ ስለሆነ ፓንቴን አላወልቅላችሁም' ማለት አይደለም የፈለኩት። 'አይዞሽ' እንዲሉኝ ብቻ። አለ አይደል እንዲታዘንልኝ ፈልጌ ነበር። ይህን ማጣቱ አናደደኝ። ከእቃ የማልሻል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ።.... ሌንጮ ግን አዘነልኝ። ወደ ታች ያወረድኩትን ፓንት ራሱ ወደስፍራው እየመለሰው 'እያመመሽ አናደርግም' አለኝ። 'ግድ የለህም አድርግ' ስለው 'ሌላ ሰው እየታመመ የምረካ ጨካኝ አይደለሁም' ብሎኝ አቀፈኝ። ራቁቴን አቅፎኝ ተኛ። ምንም አይነት ወሲባዊ ዝንባሌ ሳያሳየኝ አደረ። በገንዘቡ የገዛኝ የወሲብ እቃ እንደሆንኩ ሳይሆን እንደ ሰው ቆጠረኝ፥ አከበረኝ።...
ይህ ላንተ ትርጉም የለውም ይሆናል። እንደ ሰብኣዊ ፍጡር መታየት ያጓጓናል። እንደ ሸቀጥ ሳይሆን እንደ ሰው መቆጠር ያስደስተናል። በገንዘብ የምንገዛ ቁስ ሳይሆን ስሜት ያለን ሰዎች መሆናችን እውቅና ሲሰጠው ደስታችን ወደር ያጣል።.... ሌንጮን 'የምትፈልገውን ሳታገኝ መክፈል የለብህም' ብዬው ገንዘቡን ስመልስለት 'እያመመሽ የመጣሽው ለሆነ ነገር ገንዘብ ቢያስፈልግሽ ነው' አለኝ፥ ተረዳኝ።.... የሚረዳኝ ሰው ረሃብ አለብኝ። ረሃቤን አስታገሰው። መታቀፍ መፈለጌን ሳልነግረው አቀፈኝ። በጭንቅላቴ ውስጥ ገብቶ የማስበውን ያወቀ ይመስል 'አከብርሻለሁ፥ መከበር ይገባሻል' አለኝ። 'የሚያከብረኝ ሰው የለም' ብዬ ሳስብ እንደነበር እንዴት እንዳወቀ መገመት አልችልም። በእቅፉ አድርጎኝ በጨዋነት ግንባሬን ሳመኝና 'እውነተኛ ጓደኞችና ሚስጥረኞች እንሆናለን' ሲለኝ እንባዬ ዝርግፍ አለ። በዛች ቅፅበት 'ይህ ሰው የወሲብ ደንበኛዬ ሳይሆን የልብ ወዳጄ ሊሆን ይገባል' ብዬ ሳስብ ነበር። 'ጓደኛሽ እሆናለሁ' ሲለኝ አለቀስኩ"

ያለምንም መደነቃቀፍ አወራች።

"ለፍላፊ ሆንኩ አይደል?" ረጅም ሳቅ አስከተለች
"ስላወራሽኝ ደስ ብሎኛል"
"ሰሞኑን እያሰብኩት ሳለቅስ ነበር። ስለርሱ ማውራት ደስታን ይፈጥርብኛል"

ከጥቂት ዝምታ በኋላ "ጠጣ እንጂ" ብላኝ በመካከላችን ለአፍታ ተፈጥሮ የነበረውን የዝምታ ጥላ አስወገደችው

"ጥያቄ መጠየቅ ይፈቀድልኛል?"
"ጠይቅ"
"ሌንጮ አሁን የት ነው"
"የለም። ሞቷል!" ድንድን ያለ አጭር ምላሽ
"ይቅርታ ፥ በእውነት ይቅርታ" የምለው ጠፋኝ
"በጣም አዝናለሁ ሊሊ" የማይመለከተኝን በመጠየቄ በፀፀት ተኮራመትኩ

"አትፀፀት፥ አልቅሼ ሃዘኑ ቀሎኛል። በፊት ስለ ሞቱ ሳስብ አለቅስ ነበር። አሁን ግን አላለቅስም"
"ቁስልሽን የነካካሁት መሰለኝ"
"እኔው ነኝ ቁስሌን የነካካሁት፥... ባይሆን አሟሟቱን ልንገርህ"
"መናገሩ መጥፎ ስሜት አይፈጥርብሽም?"
"በፍፁም! ይልቅ ያጀገንኩት ስለሚመስለኝ ኩራት ቢጤ ይዳስሰኛል"
"ጥሩ.... ንገሪኛ"
"በኦሮሞ የፖለቲካ ተቃውሞ ወቅት እሬቻ ክብረ በኣል ላይ የሞቱትን ሰዎች ታስታውሳለህ?"
"በሚገባ እንጂ"

"ሌንጮ ከነርሱ መካከል ነው። እንደ ነገ ወደ ቢሾፍቱ ለመሄድ እንደ ዛሬ የመጨረሻውን አዳር አብሮኝ አደረ። ርህራሄውን፣ አክብሮቱን፣ ጨዋነቱን ትህትናውን አሳየኝ። ለሰዎች ሁሉ ያለውን ልባዊ ክብር ገለጠልኝ።..... ቆማጣ ሳይፀዳዳ በፊት ከጓደኞቹ ጋር ተደዋውሎ ወደ ቢሾፍቱ ሲጓዝ ስጦታ እንደሚያመጣልኝ ቃል ገባልኝ። በልቤ 'ስትመለስ ክፍያ የሌለው ንፁህ ወሲብ እናደርጋለን' አልኩ።..... ቀጥሎ ምን እንደሆነ ታውቃለህ አይደል? በክብረ በአሉ ስፍራ ወጣቶች አገዛዙን በመቃወማቸው በተፈጠረ ግርግር ሌንጮ ላይመለስ አንቀላፋ"

"አዝናለሁ"

"ሌንጮ የፍትህ መጓደል የሚያሳዝነው ሃቀኛ የዴሞክራሲ ታጋይ እንደሆነ ነብሴን አስይዤ እወራረዳለሁ። በአንዲት ለሊት የፍትህ ሰው እንደሆነ አሳምኖኛል።... ይህን ሳወራ የማላለቅሰው ስለማላዝን ይመስልሃል? አይደለም። አዝናለሁ፥ ይናፍቀኛል። የሚያደርጋቸው ባርኔጣዎች ይናፍቁኛል። ረዥም ቁመቱ ይናፍቀኛል፥ በአግባቡ የተደረደሩት ነጫጭ ጥርሶቹ ይናፍቁኛል። ግን ደግሞ ለፍትህ የተሰዋ ስለሚመስለኝ እፅናናለሁ"


@Tfanos

Читать полностью…

Tesfaab Teshome

የሆነ ሰሞን ፌስቡክን የተቆጣጠረች ወዶገብ አማራ ነበረች። አማራ በሆነች ማግስት ጀምሮ ሳር ቅጠሉን ከአማራጋ ታገናኝ ነበር። ነገረ ስራዋን ስመለከት አፍንጫዋን በቡጢ እንድምታት የሚገፋፋኝ መንፈስ ነበር ፥ ገሰፅኩት።

ሰሞኑን አንዲት ወዶገብ ኦሮሞ አለች። ሰሞኑን ኦሮሞ የሆኘች ይመስለኛል። 'ኦሮሞ ፥ ኦሮሞ ፥ ኦሮሞ' ትላለች። ለሷ እኔ ታከትኩ።

ብሔራቸው የሆነ ቀን በራዕይ የሚገለጥላቸው ሰዎች ያሉ ይመስለኛል። ብሔራቸውን ካወቁ ማግስት ጀምሮ "ብሔሬን እወቁልኝ" ዘመቻ ይከፍታሉ።

አንዳንዶች ደግሞ ለሆነ ብሔር በፈቃድ የሚሰለፉ ወዶገብ ናቸው። እኒያ 'ከጳጳሱ በላይ ልሁን' ከሚል ጀማሪ አማኝ ይመሳሰላሉ። ሲያሸበሽቡ ወደር የላቸውም

"እኔ እኮ በብሔሬ አላፍርም እወቁልኝ" ማለት የሚያበዙ ሰዎች ሊነግሩን የሚፈልጉት በማንነታቸው የሚኮሩ እንደሆኑ ነው። እውታው ግን እወቁልኝ እያለ ከጣሪያ በላይ የሚጮህ ሰው ያልሞላው ባዶነት አለበት። ባዶ ጣሳ መጮህ ይወድ አይደል?

በማንነቱ የሚኮራ ሰው ምስክር አያሻውም። 'ኑ በማንነቴ እንደምከራ መስክሩልኝ' እያለ እኝኝ የሚል በራስ መተማመኑ የተሰለበ ነው።

@Tfanos

Читать полностью…
Subscribe to a channel