"ሚስቴን የተመለከተብኝ ይገደ.ል"
* * *
ፍቅር ወለድ ቅናት ስልጣን አያግደውም፥ ዙፋን አያሸንፈውም፥ መንበር አይረታውም።
አፄ ቴዎድሮስ በአንድ ወቅት አለቃ እና ከልካይ የሌለባቸው ንጉስ ነበሩ። ንጉስ ብቻ ሳይሆን ሚስታቸውን የሚያፈቅሩ ንጉስ ናቸው። ማፍቀራቸው ደግሞ ሃይለኛ ቅናት የተቀላቀለበት ነው።
የነገራችን አስረጅ እንዲሆን የጳውልስ ኞኞን "አጤ ቴዎድሮስ" መፅሐፍ ምስክር ጠርተን ወጋችንን እንለጥቅ
ቴዎድሮስ ጉዞ ሲኖራቸው ንግስቲቱ አብራቸው አይጓዙም። አይጓዙም ሲባል ከጉዞው ይቀራሉ ማለት አይደለም። ንግስቲቱ እና አሽከሮቿ ከንጉሱና ጭፍሮቹ ራቅ ብለው ይከተላሉ። ንግስቲቱ ሰው እንዳያያቸው ይከለላሉ። ከዛም ፆታዊ ግኑኝነት መፈፀም በማይችሉ ጃንደረባ ወታደሮች ይታጀባሉ። ነገሩ አስቂኝ መስሎ ቢታይም የዚህ ሰበብ ወንድ አይኑን ወደ ንግስቲቱ እንዳይጥል ነው። በአጭሩ የንጉሱን ተፈቃሪ ሚስት ማየት ክልክል ነው!
ከእለታት በአንዱ ወደ ንግስቲቱ ድንኳን አንድ ወታደር አቀና። ከንግስቲቱ አሽከር ጠጅ ሲለምን እጅ ከፍንጅ ተይዞ ወደ አጤ ቴዎድሮስ ተወሰደ።
"ምን ልትሰራ ባለቤቴ ድንኳን ጋር ሄድክ?" አሉ ቴዎድሮስ በቁጣ
"ጠጅ ፈልጌ" አለ አሽከሩ እየተርበተበተ
"ውሸት ነው። ሚስቴን ሰርቀህ ለማየት ነው"
"እረ አይደለም"
"የኔን ሚስት ማየት ክልክል መሆኑን አታውቅም?"
"በሚገባ አውቃለሁ ጌታዬ"
"ምናባህ ቆርጦ እሷ ዘንድ ሄድክ ታዲያ"
"ጠጅ ፍለጋ"
(ውይይቱ ቃል በቃል ይኸን የሚመስል ባይሆንም በምናብ ውይይቱን ፈጠርነ)
ወታደሩ ጠጅ ወዳድ መሆኑ እና የንግስቲቱን መልክ ለማየት አለመሄዱ ከተረጋገጠ በኋላ ቴዎድሮስ ማሩት። ድርጊቱ ሞት የሚያስቀጣ ቢሆንም በ50 ጅራፍ ግርፋት አለፉት
@Tfanos
@Tfanos
ትላንት፥ ዛሬ፥ ነገ
* * *
ትላንት:-
የሃይማኖት መንፈስ፥
በስልጣነ መንበር ፥ ስለተሰየመ
ምክኒያትን ሊጨቁን ፥ ሃይልን ተጠቀመ
ደግሞም:-
ስለህልውናው ፥ምክኒያት ተፋለመ
በብዙ መጋደል፥
እርሱ 'ሚዘውረው ፥ መንግስትን አቆመ
ዛሬ:-
ቀድሞ ሎሌ ሳለ ፥ ስለተበደለ
ምክኒያት ገዢ ሲሆን ፥ በሃይል ተበቀለ
ሃይማኖት ዙፉኑን ፥ ስለተነጠቀ
በበቀል ቡጢዎች፥ አቅሙ ደቀቀ
ነገ:-
በመፋለም ብዛት ፥ እጅግ ይዝላሉ
ጎዶሎን 'ሚሞላ ፥ አጋዥን ይሻሉ
ከዛም:-
ሃይማኖት ከሳይንስ ፥ እርቅን ይፈጥራሉ
ስሜት ከአመክኒዮ ፥ ይተባበራሉ
ልብና አእምሮ ፥ ይተጋገዛሉ
የተፋለሙቱ ፥ አብረው ይቆማሉ
(Repost
@Tfanos
ንግድ ባንክ ምዝበራ ላይ ተሰማርቷል። ዜጎች በአደራ ካስቀመጡት ገንዘብ በማንአለብኝነት መቁረጥ ሌ.ብነት ነው።
ባንክ ገንዘብ የምናስቀምጠው በአደራ ነው። ድንገት ብድግ ብሎ 'በየወሩ 5 ብር እቆርጣለሁ' ማለት አደራን ማጉደል ነው።
መንግስት ከቸገረው ፖሊሲ ያሻሽል ፥ አላስፈላጊ ወጪ ይቀንስ ወዘተ።ነገር ግን በመንግሥት ተቋማት በኩል የዜጎችን ገንዘብ ግን አይዘረፍ !
@Tfanos
"በተሰፋዬ ገብረአብ አማራ ተገ.ደ.ለ"
* * *
ሰሞኑን የተስፋዬ ገብረአብን ህይወት የሚያትት መፅሐፍ መፃፉን ተከትሎ አንዳንድ የዋህ ሰዎች ለእልፍ አማራ መሳደድ እና መፈናቀል ሰበቡ ተስፋዬ እንደሆነ እያብራሩ ነው። ደፋር ድምዳሜ እንደመስጠት ካልተቆጠረ በቀር በችግሩ ላይ የተስፋዬ አስተዋጽኦ 1 ፐርሰንት ይሆናል ብዬ አላምንም። አዎ አላምንም!
ለብሔርተኝነት ማበብ፥ ለአማራ መሳደድ መሰረት የተጣለው ተስፋዬ ከመወለዱ በፊት ነው!
አልቤርቶ ስባኪ የፋሽ.ስት ወረ.ራን አስመልክቶ ጠቃሚ መፅሐፍ ፅፏል። መፅሐፉ በርካታ ቁም ነገሮች ያካተተ ሲሆን አንዱ ጉዳይ ፋሽ.ስት ኢትዮጵያን በብሔር ለመከፋፈል የሄደበት ርቀት ነው። አሻሚ ባልሆነ መንገድ የአማራው ማህበረሰብ ተለይቶ እንዲጠቃ የሚያደርግ ፕሮፖጋንዳ እና ፖሊሲ በጣሊያን በኩል ተተግብሮ ነበር። ያ የመ.ርዝ ዘር አመታትን የሚሻገር ሆኗል። ያዘጋጇቸው ሰነዶች እና ያበጃቸው የጥላቻ መስመሮች በየዘመኑ ድጋፍን እያገኙ ዳብረዋል።
'ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር' በሚለው መፅሐፍ በፋሽ.ስት አሳሳች ፕሮፖጋንዳ ተገፍተው የአማራ ተወላጆች እና የኦርቶዶክስ አማኞች በሀረር አከባቢ የደረሰባቸው ጥቃት ተሰነዷል። በግልፅ ቃል ፋሽ.ስት ለአማራ መሰደድ እና ለብሔር ክፍፍል ምቹ መደልድል ሰርቷል።
የያ ትውልድ አባላትም ለአማራ መታረ.ጃ ቢ.ላ በመሳል ተሳትፈዋል። የዋለልኝ መኮንን ፅሁፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ በወቅቱ ለመብት እንታገላለን የሚሉ ወገኖች በአሳፋሪ ሁኔታ ፀረ አማራ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። መረራ ጉዲና በግልፅ በመፅሐፉ እንደመሰከረው አማርኛ መናገር እንኳ የሌላው ብሔር ጠላት እንደመሆን እስከመታሰብ ደርሶ ነበር።
የያ ትውልድ አባላት ተፅዕኗቸው በዘመናቸው የተገደበ አልሆነም። ዘመን ተሻግረው የኛን ትውልድ የፖለቲካ አቅጣጫ ወስነውታል። ሕገመንግስት አዘጋጅተዋል፥ ተቃዋሚ ፓርቲ መስርተዋል፥ ሚዲያ መርተዋል። ትላንት ግልፅ የሆነ የአማራ ጥላ.ቻ የነበራቸው ወገኖች ዛሬ ሚዲያ እና መንበር ሲያገኙ፥ ተቃዋሚ ፓርቲ ሲመሩ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሰብ ወስብሴቤ አይደለም!
በምርጫ 97 ወቅት 'ቅንጅትን ማን ይምራ' የሚል ውይይት ተደርጎ ነበር። አስገራሚው ነገር 'አማራ ቅንጅትን መምራት የለበትም፥ ምክኒያቱም አማራ መሪ ከመረጥን ዘመቻ ይደረግብናል' የሚል ሃሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም በብዙ ክርክር ሃይሉ ሻውል ተመርጧል። ፍሬ ነገሩ አማራ መምራት የለበትም የሚል ክርክር መቅረቡ ነው። ይህ ብዙ ይናገራል።
ብርሃኑ ደቦጭ 'የድንቁ.ርና ጌቶች' በሚለው መፅሐፉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአማራ ተወላጅ ሹመት እንዳያገኝ የቀረበን ሃሳብ አስፍሯል።
የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሩቱ ፀረ አማራ አቋም ማራመዳቸው ፥ አማራ ጠል ያልሆኑቱ ደግሞ 'አማራ መሪ ከሾምን እንሳደዳለን' ማለታቸው ብዙ የሚነግረን ነገር መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ትውልድ ይቀርፃሉ የሚባሉ የዩኒቨርስቲ ማህበረሰቦች ከአማራ በተፃራሪ መቆማቸው ልብ ያደማል።
ከሁሉም በላይ መታወቅ ያለበት እውነት አለ። በመዋቅር ያልተደገፈ ጥ.ላቻ ጉዳቱ ዝቅተኛ ነው። የመዋቅር ድጋፍ ሲታከል ግን አውዳሚ ይሆናል።
በሩዋንዳ ቱቲ.ሲዎች ሲጨፈ.ጨፉ የሀገሪቱ መንግስት የጥ.ቃቱ ደጋፊ ነበር። በአውሮፓ አይሁዶ ች ሲገደ.ሉ መሪው ና.ዚ ነው። በኢትዮጵያ አማራ ሲሳ.ደድ ገዢው ፓርቲ አመቻችቷል። ከበደኖ ጀምሮ የተደረጉ የአማራ ጭፍጨ.ፋዎች በሚያሳዝን ሁኔታ የኢህአዴግ እጅ ነበረበት። ዛሬም ያው ነው።
በእርግጥ የተስፋዬ መፅሐፍ አስተዋጽኦ ካለው አስተዋጽኦው ሽራፊ ነው። ከተስፋዬ በተቃራኒ በመሆን ትርክቱን ሊሞግቱ ለሞከሩት ሚዲያ የከለከለው ማነው? ፖለቲከኞች የሚያቀርቡትን መከራከሪያ ሊሞግቱ ለሚፈልጉ የታሪክ ተመራማሪዎች መጫወቻ ሜዳ የነሳው ማን ነው?
ምን እያወራሁ ነው? የችግሩን ምንጭ ሳይረዱ መፍትሄ ማግኘት አይቻልም። እውነተኛ መፍትሔ የሚፈልግ የችግሩ ምንጭ ላይ ያተኩር።
ባንክና ታንክ ያለው አካል ፥ መዋቅር የመዝጋት ስልጣን ያለው መንግስት ፥ አክራ.ሪ መገኛ ብዙሃን ፥ተቋማት፥ ፓርቲዎች ወዘተ በአማራ ላይ ምን ሲሰሩ ነበር?
የችግሩ ምንጭ ያለው ሌላ ቦታ ነው።
መውጫ ፥ ከተስፋዬ ስራዎች 'የሰራዊቱ ገመና' ይበልጥ ደስ ይለኛል። ቀጥሎ 'ያልተመለሰው ባቡር'ን እወዳለሁ። 'የቡርቃ ዝምታ'ን በተመለከተ በእውቀቱ ስዩም 'ከአሜን ባሻገር' ላይ ያቀረበው ትችት ያሳምነኛል።
በተረፈ 'የቡርቃ ዝምታ' የራሱ አሉታዊ አስተዋጽኦ ሊኖረው ቢችልም የአማራ መሳደድ ምንጭ ግን ሌላ ነው!
@Tfanos
ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ከ100 አመት በፊት የተፃፈ "መንግስት እና የህዝብ አስተዳደር" የሚል መፅሐፍ አለው። በመፅሐፉ "ኢትዮጵያዉያን አስተዳደሩን አላወቅንበትም እንጂ ብዙ ገንዘብ አለን። መቶ ሚሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ አለ በሐገራችን" ብሎ ነበር።
ነጋድራስ መቶ ሚሊዮን ብር እንደ ሐገር ብዙ መሆኑን ያኔ ፅፏል። አንዲት እህታችን ደግሞ ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ መቶ ሚሊዮን የአንድ ሰው ሀብት መሆን አለበት እያለችን ነው።
ልክ ናት። መቶ ሚሊዮን ብር አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ቤት እና መኪና ገዝቶ ጥቂት ቢተርፍ ነው። ከመቶ ሚሊዮን በታች ያለው ሃብታም አይደለም ማለቷ አግባብ ነው።
ይልቅ በአንድ ክፍለ ዘመን እድሜ የተፈጠረው ልዩነት ያስደነግጣል። የሆነ ዘመን መቶ ብር ብዙ ነበር። አሁን ዋጋ አጥቷል።
እሷን መስደቡን ትቶ የገንዘብን የመግዛት አቅም አሽመድምዶ ባዷችንን ያስቀረውን አካል መቆጣት ይሻሌል። እሷማ ልክ ናት።
በዚህ አካሄድ ለወደፊቱ ደሃ ሚሊየነሮች ይፈጠራሉ። ምንም የማይገዛ ሚሊየን ብር ይኖረን ይሆናል
@Tfanos
"ኮለኔል መንግስቱ ግድያን የብሔራዊ ፖሊሲያቸው ማስፈፀሚያ ምሶሶ ያደረጉት ለምንድነው ? በፖለቲካ አስገዳጅነት ወይስ እንዲሁ በተራ ጭካኔ ? ለምሳሌ ጀነራል አማንን እንውሰድ። 'ስልጣናችሁን አልፈልግም' ብለው ሄደው ቤታቸው ቁጭ አሉ። በቃ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ ማለት ነው። ይህንን ለህዝብ መንገር ብቻ ነው። ይህንን ማድረግ ሲገባ ለምን ቢሮ አልገባህም ተብለው እስራት ተፈረደባቸው። ከዚያ ሞት። ዘግናኝ ጭካኔ ነበር። እና መንግስቱ ለምን ጨካኝ ሆኑ?" /P 103/
"... [መንግስቱ] ከሙህራን ጋር ሲሆኑ በውስጥ ስጋታቸው መሀይም ናቸው። ከጀነራሎች ጋር ሲሆኑ የበታች ምንዝሮች ናቸው። ከረጃጅሞች ጋር ሲሆኑ አጭር ናቸው።የሰውን መስፈርት ሳያውቁት ተቀበሉትና ከቀያዮች ጋር ሲሆኑ ደግሞ ጥቁር ናቸው። ከጥቁሮች ጋር ሲሆኑ ደግሞ የአፍንጫና የከንፈር ጥያቄ ይነሳል። ይነስም ይብዛ ይሄን ልዩነት ሁሉ ያደበዘዙበት መድረክ ደርግ ነበር። ደርግ ደግሞ በርካታ የበታች ሹሞችን ይዟል። የትምህርት ቤት ደጅ ያልረገጡም ሞልተውበታል። ንግግር የማያውቁ ፣ ፍጥነት የሚጎድላቸው ገራገርና ኋላቀር አባላት ይበዙበታል። በዚህ መድረክ ላይ መንግስቱ አውራ መሲህ ሆኑበት። መድረኩ ትልቋን ኢትዮጵያ የመምራት ጉዳይ ሲሆን ግን እጅግ ጠበባ ነው። ጠቦ ጠቦ የፍየል ግንባር ያክላል። ታዲያ ልዩነቱ እንዴት ይጠበብ? ያለምንም ክርክር በጭካኔያዊ በቀል..." /p108/
"ኮለኔል መንግስቱ ሥልጣናቸው ከዘር ሀረግ የተመዘዘ አይደለም። እንዲያውም አብዮቱን አብዮት ሊያሰኝ ከሚችል ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል የወጡ ናቸው። ውስጡን ለቄስ ይሁን እንጂ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሪፐብሊክ ለማወጅ ታሪክ እድል ሰጥቷቸው ነበር። አልተጠቀሙበትም። በባህሪያቸው ያለ ግጭት መኖርና መምራት የማይችሉ መሪ ናቸው። ይህ አስተሳሰብ ጠመንጃ አምላኩ አደረጋቸው። ሲረሽኑ እና ሲያስረሽኑ የመሪነት ብቃታቸው የተረጋገጠ ይመስላቸዋል። ብዙ ኢትዮጵያዊያን ከቀደምት ነገስታት ሁሉ የከፋ ጨካኝ መሪ ከመሀከላቸው መብቀሉ ያሳዝናቸዋል። እንቆቅልሽ ይሆንባቸዋል። ስለዚህ ህዝቡ ከአንድ የጥንት ክፉ ንጉስ ለይቶ አያያቸውም" /p235/
ከሀብታሙ አለባቸው "የቄሳር እንባ" መፅሐፍ የተወሰደ
@Tfanos
ስጦታ ከእስር ቤት
* * *
"በአሁኑ ወቅት የእኛ የምንለውና ሁላችንንም የሚያስማማ ሕገመንግሥት ካለመኖሩ በላይ በሀገራችን ያለው የበለጠ አሳሳቢ ችግር የሕገመንግስታዊነት አለመኖር መሆኑን እገነዘባለሁ። ማለትም ከነችግሮቹም ቢሆን አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገመንግሥትም ሆነ የበታች ሕጎች በአግባቡ በስራ ላይ የሚውሉበት ሁኔታ ቢኖር ኖሮ ብዙዎቹ ችግሮቻችን በብዙ መጠን በተቃለሉ ነበር። [.....] በእኔ እይታ ሌት ተቀን ብንሰራም በቀላሉ ልናሳካው የሚቸግረን ከጥሩ ሕግ መኖር በላይ የሕገመንግስታዊነት መኖር ነው" /P7/
"ለሀገሪቱ ሕገመንግሥትም ሆነ ለወንጀልና ለፍትሃብሔር ሕጎቻችን አንዳንድ ጠቃሚ ልምዶችን ከውጭ እየቀሰሙ ማምጣት መልካም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕጎቹ በዋናነት መመንጨት ያለባቸው ግን ከራሳችን የቆዩ ልማዳዊ ሕጎች ልዩ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ መሆን አለበት" /P10/
"በፖለቲካ ሂደት የማናምንበትን ሃሳብ የምንቀበወለው ወደን ብቻ ሳይሆን ለሀገር ደህንነት እና ጥቅም ሲባል ልንከፍለው የሚገባን ዋጋም ጭምር ስለሆነ ነው"
"ዊኒስተን ቸርችል እንዳለው 'ዴሞክራሲ ከሌሎች አማራጭ ስርኣቶች የተሻለ ሆኖ የተገኘ ነገር ግን በራሱ አስቀያሚ የሆነ ስርኣት ነው'። ዴሞክራሲ በቁጥር መጠን መብዛትን ዋና መመዘኛ በማድረግ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ አመለካከትና አቋም ያላቸውን ሰዎች መሪና ገዢ የሚያደርግ ፣ ሰዎች ባመኑበት ብቻ ሳይሆን ባለመኑበት ሃሳብም ጭምር እንዲኖሩ የሚያስገድድ ስርኣት ነው" /p13/
"በሃገሪቱ ውስጥ የራሳቸውን ማንነት በብሔር መመዘኛ ማየት የማይፈልጉ እና የተለያየ ውህድ ማንነት ያላቸው በአስርተ-ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ባሉበት ሀገር ፣ የሀገርን ሕገመንግሥት ሁሉንም የሀገሪቱን ዜጎች በእኩልነት እና በአጠቃላይ የማይወክሉ 'የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች' ወኪል ነን የሚሉ ፖለቲከኞች የሕገመንግስቱ ብቸኛ አፅዳቂም ሆነ ባለቤት የሚሆኑበት ፖለቲካዊ አመክኒዮ ሊኖር አይችልም" /p 25/
ከልደቱ አያሌው "ስጦታ ከእስር ቤት" መፅሐፍ የተወሰደ
(ልደቱ ይኸን መፅሐፍ የፃው በእስር ቤት ሳለ በመሆኑ ርዕሱ 'ስጦታ ከእስር ቤት' ሊባል ችሏል። መፅሐፉ አማራጭ ሕገመንግሥት ጭምር ነው)
@Tfanos
ግራ የሚገባ ነገር አለ።
የኢትዮጵያ ህዝብን በሞላ ደፍጥጦ በአንድ መፈረጅ የስልጣኔ ምልክት የሚመስላቸው አሉ።
ህዝቡ ምንም የማይገባው አለአዋቂ ፥ ርህራሄ የማያውቅ ክፉና ጨካኝ ፥ አንዳች በጎ ነገር የማይገኝበት ፥ ሁሉም መጥፎ ነገር በገዛ ጥፋቱ የገጠመው ፥ የኋላቀሮች አውራ አድርጎ የመፈረጅ በሽታ ያለባቸው አሉ።
ህዝብ ይሳሳታል። መወቀስ አለበት። እንደማህበረሰብ ሊታረሙ የሚገባቸው በርካታ እንከኖች አሉብን።
ነገር ግን አንዳንድ ግብዝ ሰዎች እራሳቸውን ከማህበረሰቡ የተለዩ አድርገው ማመናቸው ሳያንስ ከሎጂክ የተጣላ ዘለፋ ህዝብ ላይ ሲያዘንቡ ማየት ያስቃልም ያሳፍራልም።
ህዝብ የወደደውን ሁሉ እየተከተሉ መጥላት ፥ ህዝብ ያከበረውን ማዋረድ ፥ የጠላውን ማፍቀር ወዘተ የእውቀት እና የስልጣኔ ምልክት የሚመስላቸው ግብዝ ሰዎች የሎጂክ ሀሁ መማር አለባቸው።
@Tfanos
የእግዜር ታናሽ ወንድም
* * *
ሻለቃ መላኩ ተፈራ ከዝነኛ የደርግ ሹማምንት መካከል አንዱ ነው። የስመጥርነቱ መንስኤ የአመራር ብቃቱ ሳይሆን የጭካኔ ደረጃው ነው።
ለእናቶች የጭንቀታቸው ምክኒያት ሆኗል፥ ለበርካቶች ከሀገር መሰደድ ሰበብ ነው፥ ተቆጥረው የማያልቁ ወጣቶችን ወደ ሞት ነድቷል።
መላኩ ተፈራ ይመር ይባላል፡፡ ሻለቃ ነው።
የልደት ዘመኑ በ1945 ዓ.ም ነው። በ1960 ገና እድሜው 15 ሳለ ሐረር የጦር አካዳሚ ገብቶ ሰለጠነ፡፡ ከዚህ በኋላ የውትድርና ህይወቱ ተጀመረ።
ደርግ ንጉሱን አስወግዶ ወደ መንበር ከወጣ በኋላ በደርግ አባላት መካከል የስልጣን ሽሚያ ሲፈጠር አሰላለፉን ከመንግስቱ ሃይለማሪያም ጋር ማድረጉ የስልጣን መንገዱን አመቻቸለት።
ከታህሳስ 15 ቀን 1969 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 1970 የጎንደር ክፍለሀገር ቋሚ የደርግ አባል፣ ከነሐሴ 1 ቀን 1970 ጀምሮ ደግሞ በጎንደር ክፍለ ሀገር ዋና አስተዳዳሪ ሆኖ ሠርቷል፡፡
ጎንደር ከደረሰ በኋላ የጭካኔ መዋቅር ዘረጋ። ልዩ እስር ቤት አቋቋመ፥ ተጠርጣሪዎች የሚሰቃዩበት የምርመራ ክፍል አደራጀ፡፡
ደግሞ ከእርሱ ትዕዛዝን የሚቀበል መቺ ኃይል መሰረተ፡፡
ሻለቃ መላኩ በጎንደር ምድር ሕግን ሽሮ ሕግ ሆነ።
"በሥራ ቀናትና ሰዓት ማንኛውም ተማሪ በከተማ ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ" የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ። ትዕዛዙን የጣሰ ሁሉ "ፀረ አብዮት" እየተባለ እንዲቀጣ ወሰነ።
'ፀረ-አብዮት' ተብለው የሚፈረጁ ሰዎች ቅጣታቸው ግልፅ ነው። ይገደላሉ! በቂ የወንጀል ማስረጃ እንደሌለባቸው እየታወቀ እንኳ ያለ ርህራሄ ይገደላሉ።
የገጠር ነዋሪዎች ወደ ከተማ ለመግባት ልዩ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ እንዲኖራቸው አወጀ። ያለ ፈቃድ ከተማ የሚገባ ገጠሬ ግን እንደወንጀለኛ እንዲታሰር ትዕዛዝ አወረደ። የማይሻር ትዕዛዝ!
ሻለቃ መላኩ ሹመኛ በነበረ ወቅት፥ ጎንደርን በደም ለውሷል። ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመላኩ ትዕዛዝ ዜጎች ይረሸኑ ነበር።
'ደርግን ተቃውመዋል' የተባሉ ዜጎች ጉዳይን በራሱ ስልጣን ይመረምርና ብይን ያስተላልፋል። ሲለው 'በእስራት ይቀጡ' ይላሻል። ካሻው የጅራፍ ግርፋትን ይወስናል። ሲፈልግ ደግሞ በስቅላት ያስገድላል። ስቅላት ሲሰለቸው በጥይት ያስደበድባል።
አገዳደልን በተመለከተ የራሱን ሕግ አውጥቶ ነበር። መንግስትን የሚቃወሙ፥ ለኢህአፓ የሚያደሉ ፥ ደርግ በማይወደው የፖለቲካ መንገድ የተራመዱ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ መመሪያ አወረደ። ጥፋተቸው ከፖለቲካ ጋር የማይገናኝ ሰዎች ደግሞ በገመድ ተሰቅለው ይገደላሉ፡፡
በሻለቃ መላኩ ትዕዛዝ የሚፈፀም ግድያ እንደ አንዳች ትርዓት ለህዝብ ይቀርባል። ግዲያ የሚፈፀመው፥ ሰው በሚሰበሰብበት የገበያ ቀን ነበር።
ለመግደል የተለየ ወንጀል አስፈላጊ አይደለም። "የሀምሳ ሳንቲም መለኪያ ሲሰርቁ ተገኝተዋል" የተባሉ ሰዎች በገበያ ቀን በህዝብ መሓል በጅራፍ ተገርፈዋል፥ በስቅላት ተቀጥተዋል።
ጎንደሬው መላኩ ጎንደርን በደም ጎርፍ አጥለቅልቋል። ወጣቱንና አዛውንቱን ያለከልካይ ፈጅቿል። ሴቶችን ባል አልባ ህፃናትን አባት የለሽ ሲያደርግ ተቆጪ አልነበረውም። ወላጆችን ያለጧሪ ሲያስቀር "ተው" ያለው አልተገኘም።
ሻለቃ መላኩ ለወሰነው ፍርድ ይግባኝ የለውም። ጊዜ ያደላለት ፈላጭ ቆራጭ ዳኛ ነው!
የሰውዬው ጭካኔ ገደብ አልባነት ያስመረራቸው የጎንደር እናቶች ብሶታቸውን በቀጣዩ ግጥም ተወጡ።
"የአዘዞ ጎመን ፥አልበላም እርም ነው
ዝናብ አይደለም ፥ያበቀለው ደም ነው፡፡
መላኩ ተፈራ ፥ የእግዜር ታናሽ ወንድም፣
የዛሬን ማርልኝ ፥ ሁለተኛ አልወልድም"
እግዚአብሔር ወንድም እንደሌለው የሚታወቅ ቢሆንም ፥ እናቶች ሻለቃ መላኩ ተፈራን 'የእግዝር ታናሽ ወንድም' አሉት።
ልጃቸው ሊገደል ሲል "ይሄን ልጅ ማርልኝ ፥ ሁለተኛ አልወልድም" የሚል ተመፅኖ ያሰሙ ነበር።
ሻለቃው ጭካኔው ድንበር የለሽ ቢሆንም የደርግ መንግስት "ቆራጥ፥ ታጋይ ፥ አብዮተኛ ወዘተ " በማለት በ1980 አ.ም ሸልሞታል። ሽልማቱን የቸረው ደግሞ መንግስቱ ሃይለማርያም ነበር።
@Tfanos
@Tfanos
#የላሊበላና አካባቢው ጥንታዊ ቅርሶች አሳሳቢ አደጋ ላይ ናቸው
"""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""
ልደቱ አያሌው
ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክኒያት በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እየደረሰ ነው። ለጦርነቱ መጀመር ምክኒያት የሆነው ፖለቲካዊ ችግር ተገቢ መፍትሄ አግኝቶ ጦርነቱ በአስቸኳይ ካልቆመ በስተቀር በመጭዎቹ ጊዜያቶች የክልሉ ህዝብ ለበለጠና ለከፋ ሁለንተናዊ የህልውና አደጋ ተጋላጭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
ዛሬ ይህንን አስቸኳይ መልዕክት ለማስተላለፍ ያስገደደኝ አንድ ልዩ ጉዳይ ነው።
ይኸውም ተወልጀ በአደኩባት በላሊበላ ከተማና በከተማዋ የቅርብ ርቀት አካባቢ ስለሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች በጣም አሳሳቢና ተዓማኝነት ያላቸው መረጃዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ በተደጋጋሚ እየደረሱኝ በመሆኑ ነው። በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እየሆነ እንዳለው ሁሉ በላሊበላ ከተማና አካባቢውም ጦርነቱ በታጣቂ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን በሰላማዊውና ባልታጠቀው ህዝብም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው። በተለይም ጥንቃቄ በጐደለው ሁኔታ በአካባቢው በስፋት እየተተኮሰ ያለው ከባድ መሳሪያ በሲቭሉ ህዝብ፣ በእንስሳትና በሰብል ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ በአካባቢው ጥንታዊ ቅርሶች ላይም ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ፈጥሯል።
በላሊበላና አካባቢው የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች ለብዙ መቶ ዓመታት የቆዩና እርጅና የተጫናቸው ከመሆኑ አኳያ እንኳንስ በከባድ መሳሪያ ጩኸት በተሽከርካሪ ድምፅና እንቅስቃሴ በቀላሉ ሊናጉና ሊጐዱ የሚችሉ ናቸው። በዚህም ምክኒያት ከብዙ አመታት በፊት ጀምሮ ቅርሶቹ ለብቻቸው እንዲከለሉና ከተሽከርካሪ ድምፅና እንቅስቃሴ እንዲርቁ ተደርገዋል።
ይሁንና በሰሞኑ ጦርነት በቅርብ ርቀት በየቀኑ በሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ጩኸትና ንዝረት ምክኒያት ቅርሶቹ ከፍተኛ መናጋት እየደረሰባቸው ነው። ያለ ጥንቃቄ በሚተኮሱ የከባድ መሳሪያ አረሮች ምክኒያትም ከላሊበላ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች የመመታትና የመፍረስ ስጋት ላይ ወድቀዋል።
እነዚህ ጥንታዊ ቅርሶች ለአካባቢው ህዝብ ታሪካዊ ቅርሶች ብቻ ሳይሆኑ ከኃይማኖቱና ከእለት-ተዕለት የኢኮኖሚ ህልውናው ጋር የተያያዙ ምትክ የለሽ ኃብቶቹ በመሆናቸው እንቅልፍ የሚነሳ ከፍተኛ ስጋት በህዝቡ ውስጥ ተፈጥሯል። እነዚህ ቅርሶች የአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በዩኒስኮ/UNESCO/ የተመዘገቡ የአለም ህዝብ ብርቅዬ ቅርሶችና ሀብቶች ስለሆኑ የሁላችንም ትኩረትና ተቆርቋሪነት ያሻቸዋል።
ስለሆነም ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች የሚያካሂዱትን ውጊያ ከአካባቢው በበቂ መጠን እንዲያርቁ፣ በተለይም መንግስት ካለበት የላቀ ኃላፊነት አኳያ ጥንታዊ ቅርሶቹን አደጋ ላይ ከሚጥል ማንኛውም ዓይነት ድርጊት እንዲቆጠብ ሁላችንም ሁለንተናዊ ግፊትና ጫና እንድንፈጥር በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
. ልደቱ አያሌው
. ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም
@Tfanos
መዳፉ
* * *
"መዳፍህን ማየት እችላለሁ?" አልኩት ድንገት
"ማስፈቀድ አይጠበቅብሽም" በትህትና እጁን ዘረጋልኝ።
"አዎ ራሱ ነው..... በደንብ አስተውዬ አይቼዋለሁ..... ራሱ ነው.. .... በጭንቅላቴ የታተመ ምስልም ነው.... ህልም ቢሆንም ከእውን ክስተት በላይ አንድ በአንድ አስታውሳለሁ " በመደነቅ ሆኜ ለፈለፍኩ።
"ይቅርታ ቀበጣጠርኩብህ" ሚጢጢ ሃፍረት በስሱ ቆነጠጠኝ።
"እረዳሻለሁ" ፈገግ አለ
* * *
ይህን መዳፍ አውቀዋለሁ። እውነት ይሄን መዳፍ አውቀዋለሁ።
ጥልቅ ጨለማ ውስጥ ነበርኩ፡፡ ሊዳሰስ በሚችል በየትኛውም የብርሃን ጉልበት የሚረታ በማይመስል ድንቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነበርኩ፡፡ ካለሁበት የሚያስወጣኝ አንዳች መንገድ አልነበረም፡፡ በዛ ላይ ደግሞ በሃይለኛ ሰንሰለት ታስሬያለሁ፡፡ እጅና እግሮቼ ከመታሰር ብዛት ሰልለዋል፡፡ በሰንሰለቱ ህመም የተነሳ አጥንቶቼ ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡
በጨለማ ውስጥ በእስር ባለሁበት ክፍል ግድግዳ ላይ ሲፃፍ አየሁ፡፡ ......
እንዴት ሊሆን እንደቻለ ባይገባኝም በብርቱ ጨለማ ውስጥ ሆኜ ፅሁፍ አየሁ፡፡
"ሟች ነሽ
ደካማ ነሽ
ራስሽን ለማዳን አቅሙ የለሽም
ርካሽ ነሽ"
ግድግዳው ላይ የሚፃፈውን ማየት ባልፈልግም ይህን ለማድረግ አቅሙ አልነበረኝም፡፡
'ራሴን ማዳን የማልችል ደካማ መሆኔን አውቃለሁ፡፡ ርካሽነቴንም አልክድም፡፡ ሞቴም ቢሆን ማይቀር ነው' አልኩ ለራሴ
የነፍሴ ቁስል ፥ የልቤ ስብራት ፥ የማንነቴ ድቀት መግለፅ ከምችለው በላይ ነበር፡፡ ይህን ሳስብ እንባ በጉንጮቼ ወረደ፡፡
ይሄኔ ግድግዳው ላይ ካለው ፅሁፍ በላይ በኩል መዳፍ አረፈ፡፡ ያኔ ይፅፍ የነበረው ብእር ወደ ሚስማርነት ተለወጠና ደነገጥኩ፡፡
'ይህ ከሳሽ ብእር እንዴት ወደሚስማርነት ተቀየረ?' አልኩ። ነገር ግን ለጥያቄዬ መልስ አልነበረኝም፡፡
ከከሳሽ ብእርነት ወደሚስማርነት የተለወጠው በመዳፉ ላይ ተሰካና ደም ፈሰሰ፡፡
ነገሩ ትእንግርት ሆኖብኛል፡፡ በግራ መጋባት ሣለው የፈሰሰው ደም ግድግዳው ላይ ያለውን የክስ ፅሁፍ አጠፋውና በምትኩ 'ነፃ ነሽ' የሚል የደም ጽሁፍ ታየ።
አተኩሬ አየሁት፡፡ ያኔ ቤቱ ከየት እንደመጣ ባልገባኝ ብርሃን መሞላት ሲጀምር የታሰርኩበት ሰንሰለት ከላዬ ወደቀ....
ሰንሰለቱ ሲወድቅ ከእንቅልፌ ባነንኩ።
ፊት ለፊቴ ተኮራምቶ የተቀመጠውን ሰው መዳፍ ለመቃኘት ሞከርኩ። በህልሜ ካየሁት መዳፍ ጋር ይመሳሰል።
አዎ ራሱ ነው..... በደንብ አስተውዬ አይቼዋለሁ..... ራሱ ነው.. .... በጭንቅላቴ የታተመ ምስልም ነው.... ህልም ቢሆንም ከእውን ክስተት በላይ አንድ በአንድ አስታውሳለሁ። የሰውዬው መዳፍ በህልሜ ያየሁት ነው።
......
@Tfanos
ወጥመድ
* * *
ጎረምሳው ወፊትን ለማጥመድ ሁነኛ መፍትሔን አግኝቷል፡፡ ወንጭፍን በመጠቀም ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ከሽፎበታልና የተሻለ ብልሃትን አበጀ፡፡ፖፖን እንደወጥመድ አዘጋጅቶ በእንጨት ካስደገፈ በኋላ እንጨቱን በረዥም ገመድ አሰሮ ፖፖው ስርና አከባቢው ላይ ጥቂት ስንዴ በመበተን የገመዱን ጫፍ ይዞ ራቅ ብሎ ተቀመጠ፡፡
ይህ መንደር ማጣት ረግጦታል፥ በድህነት ተጨቁኗል፥ በአምላክ ተረስቷል፡፡ መታረዝ መገፋት ለመንደሩ ነዋሪ የህይወታቸው አንድ አካል ነው፡፡ ጎረምሳው የመንደሩ ፍሬ ነውና በመታረዝና በመራብ መኖር ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡
ሲነጋ የመንደሩ ልጆች እርግጫ አባሮሽ ለመጫወት ሲሰናዱ እርሱ ወፍን ለማጥመድ ተሰናዳ፡፡ ወንጭፍን በመጠቀም ወፍን ለማደን ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም አልሰመረለትምና በፍሬ አልባ ልፋቱ በመታከት ሌላ መፍትሔን አበጀ፡፡በወንጭፍ ጉልበት ያልተያዘችውን ወፍ በፍላጎቷ በኩል ሊይዛት ወሰነ፡፡
"ቀላል ነው" አለ በመጀነን ስሜት፡፡
"ቀላል ነው፡፡ በፍላጎት በኩል ገብቶ መማረክ! ሁሉም የፍላጎቱ ሎሌ ነውና የሚፈልገውን በመስጠት ባሪያ ማድረግ ይችላል፡፡ 'ማን ምን ይፈልጋል?' የሚለውን ማወቅ ነው ትልቁ ጉዳይ፡፡ ከዛ በኋላ ቀላል ነው፡፡ ጥሩ ወጥመድ ጉድለትን በመሙላት ይጀምራል፡፡ ጎዶሏቸው የሚሞላ፥ ፍላጎታቸው የሚሰምር የሚመስላቸው መጠርጠር ያቆማሉ፡፡ ያኔ የሚባክን ጊዜና ጉልበት አይኖርም፡፡...... ፍላጎትን የመሙላት ወጥመድ!" ውጥኑን ሲያስብ ፈገገ፡፡
ልዝብ ድል አድራጊነት እና ጠይም ኩራት ልቡን ዳሰሱት።ተርቦ ያውቃልና የተራበ መብልን ለማግኘት ባለው ጉጉት ወደሞት ቀጠና ወደሚወስደው ወጥመድ በቀላሉ ሊገባ እንደሚችል ይገነዘባል፡፡ ከውስጥ የሚመነጭ ፍላጎትን በቀላሉ መግራት እንደሚያዳግትና ያልተገሩ ፍላጎቶች ለወጥመድ እንደሚዳርጉ ይገባዋል፡፡
***
ወፊቱ ወረደች፡፡ ወፏ ምናልባት ተርባ ሊሆን ይችላል፥ ምናልበት የመልቀም ፍላጎት በተፈጥሮ የተቸራት ሊሆን ይችላል፡፡
ረሃቧን አልያም ተፈጥሯዊ ፍላጎቷን የሚያሟላ የመሰላትን ስንዴ ለመልቀም ወረደች፡፡ ከብዙ ጥቃት ያመለጠችው ወፍ በገዛ ፈቃዷ ወደ ወጥመዱ ተጓዘች፡፡
አጥማጁ ብልህ ነው፡፡ ረሃብን በማስታገስ፥ ፍላጎትን በመሙላት ሰበብ ወጥመድን አበጀ፡፡
ወፊቱ ስንዴውን እየለቀመች ወደ ፖፖው አቅጣጫ አቀናች፡፡ ሙሉ ለሙሉ በወጥመዱ ውስጥ ከገባች አጥማጁ ገመዱን በመሳብ ብቻ ግዳይን ይጥላል፡፡ ከዛን በኋላ ወፊትን ቢፈልግ ለሁል ጊዜውም አስሮ ያኖራታል፥ ቢፈልግ ይገድላታል፥ ቢፈልግም አርዶ ይበላታል።
ከወጥመዶች ሁሉ አደገኛው ወጥመድ በፍላጎት በኩል የሚመጣ ሽንቁርን የሚደፍን ጎዶሎን የሚሞላ ረሃብን የሚያስተግስ ለችግር መፍትሔ የሚመስል ወጥመድ ነው!
@Tfanos
"አማርኛ መናገር ፀረ አብዮት ነው"
* * *
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነገር ግራ አጋቢ ነው። በተለይ የያ ትውልድ አባላት የፖለቲካ አሰላለፋቸው ግራ ዘመም ከመሆኑም እኩል ነገረ ስራቸውም ግራ አጋቢ ነው። ስለመብት ቢያወሩም መብት ረጋጭ ናቸው፥ ስለ ብዝሃነት ሰብከው ሲያበቁ ጨፍላቂ ይሆናሉ።
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና 'የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች' የሚል መፅሐፍ አለው። መኢሶንን መአከል አድርጎ የያ ትውልድ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ያወሳል።
በመፅሐፉ ከሰፈሩ ገጠመኞች መካከል አንዱ 'አብዮት አምጪ' የተባለው ትውልድ ለአማርኛ ቋንቋ ያለውን የተንሻፈፈ ምልከታ እና ጥላቻ ያሳያል።
በ1966 በአርት ፋከሊቲ የተማሪዎች ተወካይ ለመሆን ውድድር ተደረገ። ከተወዳዳሪዎቹ መካከል አንዱ የነበረው ግርማቸው እጅግ አስደናቂ ንግግር በአማርኛ አደረገ። ነገር እንዳይመረጥ ተደረገ። እንዳይመረጥ የተደረገበት ምክኒያት በአማርኛ ንግግር ማድረጉ ነው። አማርኛ መናገር አድሃሪነትና ፀረ አብዮተኝነት መስሎ ስለሚታይ ንግግሩ መቅረብ የነበረበት በእንግሊዝኛ ነበር።
ግርማቸው በአማርኛ ንግግር ሲያደርግ ያጨበጨቡ ተማሪዎች ነበሩ። ነገር ግን ስመ ገናናው 'አብዮተኛ' መለስ ተክሌ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ደነፋ። "ይህ የደብተራ ልጅ ፥ በታጋዮች ደም በተገነባው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መድረክ ላይ ቆሞ የሚተፋውን ሰምታችሁ እንዴት ታጨበጭባላችሁ" በማለት ተቆጣ።
በመለስ የቁጣ ንግግር መሰረት ፥ አማርኛ የደብተራ ልጆች ቋንቋ፥ የአብዮቱ ተፃራሪ ሆኖ ተፈርጇል።
አሳዛኙ ነገር፥ ግርማቸው በአማርኛ ንግግር በማድረጉ የተነሳ ሳይመረጥ መቅረቱ ነው። መረራ በመፅሐፉ ገፅ 29 ላይ "ባልተፃፈ ሕግም ቢሆን በዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ስብሰባ ላይ በአማርኛ መናገር ክልክል የሆነበት ዘመን" በማለት ወቅቱን ገልጿል።
ያኔ እንዲህ ያሉ የተንሻፈፉ ምልከታዎች የነበራቸው "አብዮተኛ" የያ ትውልድ አባላት የዛሬውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አቅጣጫ መወሰን ችለዋል።
@Tfanos
በቅርቡ የትግራይን መርዶ ሰምተን ነበር። በሰሜኑ ጦርነት ትግራዋይ ያለፈበትን ሰቆቃ ተመልክተን አዝነናል።
አሁን ከኤርትራ ጋር ጦርነት ለመግጠም ማሟሟቅ ተጀምሯል። የውጊያ ፊሽካ ተነፍቶ ጦርነት ከተጀመረ ጦርነቱ ከሚያካልላቸው ስፍራዎች አንዱ የትግራይ አከባቢ ነው።
በትግራይ ሜዳ ፍልሚያ ይደረጋል
በግልፅ ቃል ቁስሉ ያልሻረው ትግራይ ሌላ መከራ ከፊቱ አለ።
@Tfanos
ሰውዬው የመጨረሻው ክፍል
* * *
"ማን እንደሆንክ ንገረኝ" አልኩት በድጋሚ ግራ መጋባቴን በሚያጋልጥ ሁኔታ፡፡
"እኔ.." ከናፍሩን ከማለቀቁ መላ አካሌ ጆሮ ሆነ፡፡
"ማነህ አንተ?"
"እኔ ኢየሱስ ነኝ"
"እ?"
"አዎ እኔ ኢየሱስ ነኝ"
እንደሞኝ ሳፈጥበት በእርጋታ ተመለከተኝ፡፡ እርጋታውና በራስ መተማመኑ ግራ ስላጋባኝ አይኖቼን ጨፈኩ፡፡
.... ለሩብ ደቂቃ ያህል ከጨፈንኩ በኋላ እያመነታው አይኖቼን ከመግለጤ "ዋው ደስ ይላል" የሚል የሴት ድምፅ ሰማው፡፡
ድምፁን ወደ ሰማሁበት አቅጣጫ ፊቴን ሳዞር ነጭ የለበሰች ባለረጅም ፀጉር ሴት "ሳምሪ የአይኖችሽን መገለጥ በናፍቆት ስንጠባበቅ ነበር" አለችኝ፡፡ ደግሜ ጨፈንኩ፡፡ ከዛ ገለጥኩ፡፡ ጨፈንኩ ገለጥኩ ጨፈንኩ ገለጥኩ....
"አይዞሽ ተረጋጊ... ሲስተር ህይወት እባላለሁ ራስሽን ለማጥፋ ከሞከርሽ በኋላ ራስሽን ስተሽ እዚህ ሆስፒታል ነበርሽ፡፡ ከግማሽ ሰአት በፊት የመንቃት ምልክት አሳይተሽ ስለነበር አይኖችሽን እስክትገልጪ እየጠበኩ ነበር......"
* * *
ሙሉ ለሙሉ ከነቃው በኋላ ሰውነቴን የተጫነኝ ድካምና አቅም ማጣት ባይለቀኝም ትንሽ ለመነቃቃት ችያለሁና በሃሳብ ተወጠርኩ፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ ቤተክርስቲያን የሄድኩት ራሴን ላጠፋ የወሰንኩ ቀን ነበር፡፡ በቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ሆኜ የሽርሙጥና ህይወት እንደታከተኝ እያለቀስኩ ለእግዚአብሔር ነገርኩት፡፡ ከዚህ በኋላ መውለድ አለመቻሌ የፈጠረብኝን ሃዘን ሳልሸሽግ አወራሁለት፡፡ በመጨረሻም እግዚአብሔርን 'እጠላሃለው' አልኩት፡፡ 'እግዝአብሔር ሆይ ህመሜ ሲበረታ አጠገቤ አልነበርክምና እጠላሃለው' አልኩት፡፡
ያን እለት ሰባኪው ስለ ኢየሱስ ግርማ ነበር የሰበከው፡፡ ስለኢየሱስ ግርማ ስሰማ ተናደድኩ፡፡ ቤት ስገባ 'ኢየሱስ ሆይ በጣም ክፉ ስለሆንክ እጠላሃለው ሁሉን ማድረግ እየቻልክ ከለላ ልትሆነኝ ስላልፈለግክ እጠላሃለው። ህመሜ ስለማይገባህ እጠላሃለው' የሚል ደብዳቤ በብጣሽ ወረቀት ላይ ፅፌ ራሴን ለማጥፋት ተሰናዳው፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ ቤተክርስቲያን የሄድኩ ቀን ሰባኪው በሞገሳም ድምፅ ስለ ኢየሱስ ግርማ ሰበከ፡፡
"ኢየሱስ ከመላእክት የሚበልጥ ስም አለው፡፡ አለማትን በቃሉ ደግፎ ያቆመ ነው፡፡ ለዘመኑ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ባለግርማ ነው...."
ይህ የሰባኪው ድምፅ እንደ አዲስ በጆሮዬ ቢያስተጋባም በአይነ ህሊናዬ ሁለት ምስሎች ይፈራረቁብኛል፡፡
ችጋር ያሰረጎደው ጉንጭ፥ የገረጣ የፊት ገፅ ፥ የተሸነታተረ ከናፍር፥ ወደ ውስጥ የገቡ አይኖች ፥ ደቃቅ እጆች ያሉት ሰውዬ 'እኔ ኢየሱስ ነኝ' እንዳለኝ ትዝ ይለኛል፡፡ ደግሞም የሰባኪው ንግግር ወደ ጆሮዬ ይመጣል፡፡
"ኢየሱስ በመጀመሪያ የነበረ ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆኗል፡፡ ከሆነው ውስጥ አንዳች እንኳን ያለ እርሱ አልሆነም፡፡ ፍጥረት ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯል...."
ደግሞ ይህን የሰባኪውን ንግግር የሚያጠፋ ምስል ይመጣብኛል፡፡ ርቃን የሆነ ወንድነቱ ጭምር ሳይሸፈን መስቀል ላይ የተቸነከረ ወጣት ምስል ይታየኛል፡፡ የሰውነቱን ቁስል በእጆቹ እንዳይነካ እጆቹ በግራና በቀኝ በሚስማር የተቸነከሩበት... የሰውነቱን ቁስል የወረሩትን ዝንቦች ማባረረር ያልቻለ በስቃይ የተሞላ የህመም ሰው ምስል ወደ አእምሮዬ ይመጣል፡፡
የሰባኪው ድምፅ ይህን ምስል ለማጥፋት ትግል የገጠመ ይመስል ያስተጋባብኛል፡፡
"በኢየሱስ ፊት ጉልበቶች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ተራሮች ለክብሩ ይዘምራሉ፡፡ ፍጥረታት ግርማውን ይመሰክራሉ፡፡ መላእክት በፅድቁ ፊት መቆም አይችሉም፡፡ እሱ ስሙ ብቻውን ከመላእክት ይበልጣል ...."
ሌላ ምስል ወደ አእምሮዬ ይመጣል፡፡ መደፈሬን ስነግረው እጆቹና ከናፍሩ እየተንቀጠቀጡ ያለቀሰ ያሳለፍኩት የህይወት ውጣ ወረድ ስቃይን የፈጠረበት ህመሜን ሳጫውው ደረቱን እየደቃ ያለቀሰ ሩሁሩህ ሰው ምስል ትዝ አለኝ፡፡
...... ድንገት ጉንጬ ከአይኖቼ በፈለቀ ትኩስ እንባ ታጠበ፡፡
@Tfanos
ኤፍሬም ስዩም "ንጉስ መሆን" የሚል ግጥም አለው። ሁሉም 'ንጉስ መሆን ቀላል ነው' ይላል። በተግባር ግን ፈተና ነው። "እንዲህና እንዲያ ማድረግ ብቻ በቂ ነው" ብሎ መተንተን እና በተግባር መከወን ይለያያል።
"ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፥ ሲይዙት ያደናግር" ይባል አይደል?
የቲክቶክ ተንታኞች ነገር እንደዛ ነው። ፍቅረኛ እንኳ የሌላቸው ሰዎች ትዳር እንዴት እንደሚመራ ይተነትናሉ። ትዳር ሳይመሰርቱ ስለ ልጅ አስተዳደግ የሚሰብኩ ተቆጥረው አያልቁም።
አንዳንድ ጉዳይ ከቲዎሪ የዘለለ ነገር ይፈልጋል። ከህይወት የሚቀዳ ልምድ የሚሹ አጀንዳዎች አሉ።
ማናችንም በምናባችን የምንስለው ውብ አይነት ትዳር አለ። ስለ ይቅርታ ፥ ስለመከባበር ፥ ስለመቻቻል ወዘተ ብዙ ልናልም እንችላለን።
ጉዳዩ ምኞትን አካል ማልበስ እንችላለን ወይ የሚለው ነው። "አዎ የተመኘነውን እንተገብራለን፥ የተናገርነውን እንኖራለን" የሚል ካለ "መጀመሪያ ኖረህ አሳየኝ" ሊባል ይገባል።
ከህይወት ሳይማሩ ህይወትን ማስተማር አግባብ አይደለም !
@Tfanos
"ሉሲ ምን ያህል እውነት ነች?"
* * *
ሰው ከዝንጀሮ መሰል ዝሪያ እንደመጣ ሲነገር መስማት አዲስ ነገር አይደለም። የዝግመተ ለውጥ አራማጆች አስረጅ አድርገው ከሚያቀርቧቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች አንዷ ሉሲ ናት።
ዘለቀ ሀይሉ የሚባል ፀሐፊ 'ሉሲ ምን ያህል እውነት ነች?' የሚል መፅሐፍ አለው። 133 ገፅ ናት። (ትላንት አነበብኳት) በመፅሐፉ የዝግመተ ለውጥን ቲዮሪ በአስረጅ ሞግቷል። እውነት ያይደለ ፥ በማስረጃ ሊዳብር የማይችል እንደሆነ ገልጿል።
ሐገራችን የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ለማስረዳት የምንጠቅሳትን ሉሲ አስመልክቶ በመፅሐፉ የተገለፁ አንዳንድ ሐሳቦችን እናንሳ
የተገኘው የሉሲ አፅም 40 በመቶ ብቻ ነው። ትንታኔ የተሰራው በዛ ላይ ተመስርቶ ሲሆን አንዳንድ ትንታኔዎች አሳሳችና ሆን ተብሎ የዝግመተ ለውጥ ሃሳብን እንዲደግፍ የተደረገ ነው።
ሉሲ ወደ ሰው የሚደረግ የዝግመተ ለውጠሰ ሽግግርን የምትወክል ተደርጋ ብትገርም ሉሲ ግን ኤፕ ናት ይላል ፀሐፊው። (ኤፕ ማለት ጭራ የሌላቸው የዝንጀሮ ዝሪያዎች ናቸው። እንደ ችምፓዚ እና ጎሬላ ያሉ ማለት ነው)
የሉሲ አንጎል ስፋት የኤፕን ያህላል ፥ የራስ ቅሏ የኤፕ ይመስላል ፥ እንደ ኤፕ ዛፍ ላይ ለመውጣት የሚረዳ አጥንት ፥ የቺምፓዚን የመሰለ ረጅም የእጅ ክንድና ረጃጅም ጣቶች ፥ ወደ ውስጥ በታጠፉ የፊት እጆች ምድርን ተደግፎ የመራመድ ተላምዶን የሚያሳይ የእጅ አንጉዋ መዋቅር ፥ የኤፓችን አይነት ከወገብ በላይ ከበድ ያለ አካል ፥ ወዘተ አላት ሉሲ። የመንጋጋ ቅርጿ እንደ ሰው 'U' መሰል ሳይሆን እንደ ኤፕ 'V' መሰል ነው። እኚህን የመሳሰሉ ነገሮች የሚያሳዩት ሉሲ ኤፕ እንደሆነች ቢሆንም አሳሳች በሆነ መንገድ ተገልፃለች ይላል ፀሐፊው። ለዚህም የተለያዩ ሳይንቲስቶችን እና የህትመት ውጤቶችን ምስክሮች አቅርቧል።
መፅሐፉን አንብቡት። ዝግመተ ለውጥን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ በርካታ መረጃዎች ያነሳል።
@Tfanos
በቲክቶክ የአስራአራት አመት ጎረምሶች ስለትዳር ፥ ስለቤተሰብ አስተዳደር ወዘተ ያስተምራሉ።
ቤተሰብ አስተዳደርን ለሌሎች ለማስተማር የተፈተነ የህይወት ልምድ ያስፈልጋል። በምናባችን ያለውን ለማውራት ከሆነማ ሁላችንም ጥሩ አይነት የትዳር አጣማሪነትን መተንተን አይከብደንም። ልዩነቱ ፈታኝ ሁኔታዎችን እና ተግዳሮቶችን ተጋፍጠን ማለፍ እንችላለን ወይ የሚለው ነው። ይህ ህይወት ይጠይቃል። ኑሮ ማየትን ይጠይቃል።
በምናብ የሳሉትን ብድግ ብሎ መተንተን የሚያስቅ ነገር ነው።
@Tfanos
ከትግራይ ነው የመጡት። መለመን አይችሉም። አለማመናቸው ያሳዝናል። በሃፍረት ፈገግታ እጅ ይዘረጋሉ።
ከትግራይ ሻሸመኔ ድረስ ያመጣቸው ጦርነት ወለድ መፈናቀል ነው። እጅ ሲዘረጉ አንዳች ሃፍረት ፊታቸው ላይ ይነበባል። ሰው ፊት የመቆም ልምድ እንደሌላቸው ያስታውቃሉ።
ዛሬም እንደልማዳቸው ሲመጡ ጓደኛዬ ልጆቻቸውን አሳየኝ። የልጆቹ ገፅታ በምቾት እንዳደጉ ያስታውቃል። ጦርነት የሚባል ጣጣ አፈናቅሏቸው መለመን እጣፈንታቸው ሆኗል
@Tfanos
"የፈለግኹትን አደርጋለሁ ፥ ማንንም አልሰማም" ማለትን እንደነፃት የሚቆጥሩ ለራስ ስሜት ብቻ መኖር በራስ መተማመን የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። አሁን አሁን እየበዙ ነው።
ማንንም አለመስማት በግልፅ ቃል ድንቁ.ርና ነው። በራስ መተማመን ማለት ራስን በመገንዘብ ለራስ ተገቢውን ክብር መስጠት ነው። መጀመሪያ ራስን ማወቅ ይቀድማል።
ለሁሉም ጆሮ መንሳት አለመሰልጠን ነው። ስልጡን ሰው ሌሎችን የሚያደምጥ ፥ የሌሎችን ሃሳብ በምክኒያት እና በመርህ ሚዛን ለክቶ የሚቀበል ወይም የሚጥል ነው።
በደፈናው ማንንም አለመስማት ግን እጅግ አደገኛ አለመሰልጠን ነው።
@Tfanos
"በሀይሉ ለሚመካ መጎናበስ ጥቃትን ለዘለቄታው ማራዘም ነው። እየተጋፈጥከው፣ ምን ቢጥልህ እተነሳህ ፣ ዳግም መጋፈጥ ፈሪ በራሱ ሃይል ጥርጣሬ እንዲያድርበት ያደርገዋል። ለአንተ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ሰው ኋይል ዘዴ ከሌለው ከእልህና ሰው ከመሆን እንደማይበልጥ እየተረዳው ይሄዳል" p75/
"....ጃንሆይ ብዙ ከፍርሃት የመነጩ የማጥቂያ አማራጭ አይናዋጅ ይሆንባቸዋል ። ክብርህን የምትወድ ከሆነ ጫማ የመሳሚያ ፕሮግራም ያዘጋጁልሃል፣ ስቃይ ያሰጋህ እንደሆነ አርባ ጅራፍ ግርፋት ካልተፈፀመ ይላሉ፤ ቤተሰብህን የምትወድ ከሆነ ደግሞ ግዞት ይበይኑብሃል። ሥልጣን ማጣት ያስፈራህ እንደሆነ 'ከስራ ውጭ ሆኖ ደጅ ይጥና' ይሉብሃል። አያፈናፍኑህም። ከንጉሥ ጋር መጣላት ከሀገር ልወደድ ባይ ጋር ጥርስ መጋባት ነው" /p76/
"የሰው ልጅ አቅምና የማጥፋት ሀይሉ የተመጣጠነ መሆኑ በጀ እንጂ በትንሽ መከፋት ስንቱን ሲገለባብጥና ከሰልፍ ውጭ ሲያተረማምስ በኖረ ነበር። የስሜት አፀፋችን ለከት አልባ መሆኑ'ተደፈርን፣ ተዋረድን' ባልን ቁጥር የአርማጌዶን ጦርነት እያስነሳንም የማንረካበት እራስ ወዳድነት ውስጣችን አለ" /p38/
አለማየሁ ገላጋይ "ቤባኒያ"
@Tfanos
".... ዛሬ ላይ ተጋኖ እንደሚነገረው የቀድሞዎቹ መንግስታት ሆን ብለው ቋንቋዎችን የማጥፋት ፖሊሲ ቀይሰው ፣ ዘመቻ አካሂደው ቢሆን ኖሮ ከ80 በላይ የሆኑት የሀገራችን ቋንቋዎች ህልውና ተጠብቆ ሊገኝ አይችልም ነበር" (p46)
"... የቅርቡን የዳግማዊ ሚኒሊክን ዘመን ብንወስድ ክልሎች በውስጥ አስተዳደራቸው ሙሉ ነፃነት ነበራቸው ለማለት ይቻላል። በልዩ ወታደራዊ ሁኔታ ከማዕከል በሚላኩ እንደራሴዎች እንዲተዳደሩ ከተደረጉት ጥቂት ክፍላተ ሀገራት በቀር አብዛኞቹ የሚተዳደሩት በራሳቸው ባህላዊ መሪዎች ሲሆን የሚጠቀሙትም በራሳቸው ቋንቋዎች ነበር። ማዕከላዊ መንግስቱ ከእነሱ የሚጠብቀው አመታዊ የግብር ግዴታቸውን እንዲያሟሉ እና በሀገር ላይ ጦርነት ሲነሳ ሠራዊታቸውን አስከትለው ከንጉሰ-ነገስቱ ጎን መሰለፍ ብቻ ነበር። ከዚህ ውጭ ማዕከላዊ መንግስት በውስጥ አስተዳደራቸው ጣልቃ መግባት የተለመደ ወይም የሚዘወተር መንገድ አልነበረም። ከዚህ ልምድ በመነሳት በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም 'በሀገራችን እውነተኛ ፌደራሊዝም የሰፈነው በአፄ ሚኒሊክ ዘመን ነበር' በማለት ገልፀውታል" (p 52)
ከፋሲካ ሲደልል 'የሻሞላው ትውልድ' መፅሐፍ የተወሰደ
@Tfanos
የቄሳር እንባ
* * *
"የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክና ትውፊት አንድ ዝንባሌ ይታይበታል። ነገስታት ወደ ስልጣን ሲወጡ ምንግዜም ይስቃሉ። የዘመነ መንግስታቸው እና የራሳቸው ፍፃሜ እውን ሆኖ ሲያዩት ደግሞ ያለቅሳሉ"
"አፄ ቴዎድሮስ በንግስና ዘመናቸው በሁለት አጋጣሚዎች ምርር ብለው ማልቀሳቸውን ታሪክ መዝግቦታል። የመጀመሪያው ባለቤታቸው እቴጌ የሞቱ እለት ነበር። ሁለተኛው ደግሞ ገብርዬን የእንግሊዝ ጥይት የበላው ቀን። የገብርዬ መሞት የአፄነት ዘመናቸው ያከተመበትን ደቂቃ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ አይኖቻቸው የእንባ ዘለላዎችን ቁልቁል ለቀቁ"
"አፄ ዮሐንስ አራተኛ እንዲሁ ሁለቴ እንዳነቡ ተፅፏል። ኩፊት ላይ ከደርቡሽ ጋር ተዋግተው ነበር። ብዙ ደርቡሾችን ማርከው እንደበግ አስነዷቸው። ውጊያውን በድል ተወጡ። ያለቀው ሰው ቁጥር ግን በሃዘን ልባቸውን ነካው። አንገታቸውን አቀርቅረው ፀሎተ ፍትሃት ሲያደርጉ እንግዳ ነገር ጆሯቸውን ሳበው። ከተማረኩት ደርቡሾች አንዱ በአማርኛ 'እረ እባካችሁ ውሃ አቅምሱን' ሲል ሰሙት። በፖለቲካ ህይወታቸው እንደዛ ቀን ደንግጠው አያውቁም። 'እንዴት፣ በል?' ጮኹ። አስጠርተው ከፊታቸው አስቆሙት"
".... 'የኛ ሰው ነህ?' በመገረም ጠየቁት። 'አዎ ነበርኩ። ጅሃድ ወጥቼ ማረካችሁኝ' መለሰላቸው። ኢትዮጵያን ጠንቅቀው ባለማወቃቸው ምክኒያት በከንቱ የፈሰሰው ደም አሳዘናቸው። አይኖቻቸው እንባ አቀረሩ። ፊታቸውን በመዳፋቸው ሸፈን ሲያደርጉት ፂማቸውን እንባ አርሶታል። ሁለተኛው እና የመጨረሻው እንባቸው ደግሞ መተማ ላይ ያለቀሱት ነው። በፅኑ ቆስለው እያቃሰቱ ነበር። ልጃቸው ዘውዱን እንዲወርስ ሲናዘዙለት እንባ ፈሰሰ። የራሳቸው እና የንግስና ዘመናቸው ፍፃሜ አስለቀሳቸው"
"ከብዙዎች የኢትዮጵያ ነገስታት በጣም ሆደ ቡቡ እና አልቃሽ ንጉስ ሚኒሊክ እንደነበሩ ተፅፏል። በ1882 'የክፉ ቀን ጊዜ' ያለቀሱት እንባ ግን የተለየ ነበር። አንዲት ሴት 8 ልጆችን እየያዘች አርዳ በላቻቸው ተባለ። ተይዛ እፊታቸው ቀረበች። 'ልጄ እውነት ሰው በልተሻል?' ጠየቋት። ሴትዮዋ ቅንጣት አላመነታችም። 'ታዲያ ሲርበኝ ምን ላድርግ? ግጥም አድርጌ በልቻቸዋለሁ' አለቻቸው። እንባቸው ከመቅፅበት ፈሰሰ። ሌላው አጋጣሚ ተከተለ"
"ከ29 የንግስና የንጉሰ- ነገስትነት ዘመናቸው በኋላ ጤና እምቢ አላቸው። ዶክተሮቹ ብዙ ሞከሩላቸው። ተሻላቸው ሲባል እንደገና ይታመማሉ። እቴጌ ጣይቱ ለፈረንጅ ህክምና ንቀት ነበራቸው። የባላቸውን ጉሮሮ አንቀው ደብረሊባኖስ ገዳም ወሰዷቸው። ሰባት ሁለት ሲያስጠምቁ ከርመው ይዟቸው ተመለሱ። ባጋጣሚ ይሁን በፀበሉ አይታወቅም ተሻላቸው። እንዲያውም ነቃ ብለው ዙፋን ላይ ተቀመጡ። በርካታ ውሳኔዎች ሰጡ። ጥቂት ቀናት ቆይተው ግን እንደገና ወደቁ። ተመልሰው እንደማይነሱ ታወቃቸው። ጃን ሜዳ የተነበበውን እና ልጅ እያሱን አልጋ ያወረሱበትን ኑዛዜ የሰጡ እለት እንባቸው አላናግር አላቸው። የፍፃሜ እንባ"
"አፄ ሃይለስላሴ ሦስቴ ሲያለቅሱ ታይተዋል። ባለቤታቸውና ልጃቸው ሲሞቱ በተለያየ ጊዜ አለቀሱ። የሚገርመው ነገር ከስልጣን የወረዱ እለት አላለቀሱም። የመጨረሻውን እንባ ያፈሰሱት ከዚያ በኋላ ነው። ሻምበል ዳንኤል አስፋው መርዝ ሊያቀምሳቸው ባለ በሌለ ጉልበቱ የታገላቸው ቀን። አገልጋያቸው ሲገባ እንባቸው ከአይንቻቸው ግራና ቀኝ እየወረደ ጉንጫቸው አርሰው አገኛቸው"
"ጥቁሩ ቄሳር /መንግስቱ ሃይለማርያም/ እስከአሁን አንዴ ሲያለቅሱ በፎቶግራፍ ተይዘዋል። .... አስመራ ሄደው ነበር። ቆስለው ማገገሚያ የገቡ ወታደሮችን አነጋገሩ። ሁለት እጆቹን ያጣ ፥ ሁለት እግሮቹ የተቆረጡ ፥ አይኖቹ የፈሰሱ ፥ ድዱ የረገፈ..... የሚዘገንን ትርዒት ነበር። ጉዳተኞች በማገገሚያ ማዕከሉ ደረሰብን የሚሉትን በደል ዘርዝረው ነገሯቸው። መንግስቱ አልቻሉም። የእጅ መሃረባቸውን ከኪሳቸው አወጡ። በትረ መኮንናቸውን በጉያቸው ሻጥ አድርገው እየየ ብለው አለቀሱ። ሻል ሲላቸው ፊታቸውን ወደ ጀነራል ተስፋዬ አዞሩ"
"... 'በሉ መንቀሳቀስ የሚችሉ ጉዳተኞችን ሰብስቡልኝ' አሉ። የማዕከሉ አዛዥ የነበሩት ኮለኔል እጃቸው ታስረው እንዲቀርብ አደረጉ። 'ይኸው ማዕረጉ ተገፎ ያለ ጡረታ ከሰራዊቱ እንባረር ቀጥቼዋለሁ'። ሁለት ወታደሮች በጠመንጃቸው ላይ ሳንጃ ሰክተው ቀረቡ። የኮለኔሉን ማዕረግ በመቀስ ቆርጠው መሬት ላይ ጣሉት። 'ቀኝ ኋላ ዙር' ብለው አዘዟቸው። ኮለኔሉ ፊታቸውን አዞሩ። ወታደሮቹ የጠመንጃዎቻቸውን ሳንጃዎች በቀኝና በግራ ሙርጣቸው ላይ ሰክተው ወደሩት። በሩጫ እርምጃ ወደግቢው በር እንዲሮጡ አዘዟቸው። እንገፍ እንገፍ እያሉ ሮጡ። ከግቢው በር አስወጥተው ሲመለሱ ቁስለኞቹ ደማቅ ጭብጨባ አሰሙ። ይህ በዚህ አለፈ።
"ልጃቸውን ትምህርትን ወደ እስራኤል ሲሸኙም እንደዚያው ትንሽ አንብተዋል"
"ኮለኔል መንግስቱ የመጨረሻውን እና ዋናውን እንባ የሚያነቡት መቼ ይሆን?....."
ከደራሲ ሃብታሙ አለባቸው 'የቄሳር እንባ' መፅሐፍ የተወሰደ።
ከገፅ 236-238
@Tfanos
'አዶልፍ ኤክማን'፥ የሞት አደላዳዩ ሞት
* * *
ሪካርዶ ክሌመንት የዘውትር ስራውን አገባዶ ወደ ቤቱ እያዘገመ ሳለ አንድ ሰው አስቆመው። ክሌመንት የሰውዬው ነገር ስላልጣመው ትቶት ሊያልፍ ሲሞክር በጫማ ጥፊ መቶት ዘረረው። ይሄኔ የመቺው ሌላ ጓደኛ ፈጥኖ ደረሰና ክሌመንትን ከወደቀበት አፋፈሱት። ሪካርዶ ክሌመንት ምን እየተደረገ እንዳለ ለማሰብ በሚሞክርበት ቅፅበት ራቅ ብሎ የቆመ መኪና አጠገባቸው ደረሰ። ሰውዬን አፋፍሰው ወሰዱት፥ ወደ ሆቴል።
ሪካርዶ ክሌመንትን አፍነው የወሰዱት በሆቴል ክፍል አስቀምጠው ምርመራ ጀመሩ።
"ስምህ ማነው?"
"ሪካርዶ ክሌመንት"
"ዜግነትህሰ?"
"አርጀንቲናዊ"
ይሄኔ መርማሪው ተቆጣ። 'አንተ ክሌመንት አይደለህም፥ አንተ አዶልፍ ኤክማን ነህ' አለው በቁጣ።
አዶልፍ ኤክማን ማለት ከሰይጣን መወዳደር የሚቀጣው ጨካኝ ሰው ነው። ኤክማን በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር መጋቢት 19 ቀን 1906 አ.ም የተወለደ ሲሆን ካደገ በኋላ ና.ዚን በመቀላቀል በርካታ ወንጀሎችን ፈፅሟል፥ ሰብአዊነት ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።
በ 1930 ዎቹ አጋማሽ አዶልፍ ኤክማን አይሁዳውያንን መከታተል አላማው ባደረገ ተቋም ውስጥ በመግባት ይሁዲዎችን ሲሰልል ነበር።
ኤክማን እጅ ረጅም ነው።
1938 እና 1939 መካከል ብቻ 110,000 የኦስትሪያ አይሁዶችን እንዳሰደዱ መደላድል ሰርቷል፥ መባረራቸውን አመቻችቷል።
ቁጥራቸው 1 ሚሊዮን 5መቶ ሺህ የሚበልጥ አይሁዶች ከመላው አውሮፓ እየተለቀሙ ወደ ግድያ ማዕከላት ሲጋዙ እሱ እጁ ነበረበት።
በ1942 ከጀሌዎቹ ጋር በመሆን ከስሎቫኪያ ፥ከኔዘርላንድስ ፥ከፈረንሳይ እና ከቤልጂየም አይሁዳዊያን እንዲባረሩ አድጓል።
በ1943 እና 1944 የግሪክ፥ የሰሜን ኢጣሊያ እና የሃንጋሪ አይሁዶች በማሳደድ ተሳትፏል።
ከኤፕሪል 1944 መጨረሻ ጀምሮ በ6 ሳምንታት እድሜ ብቻ 440,000 የሚሆኑ የሃንጋሪ አይሁዶችን ከሀገር እንዲባረሩ ቁልፍ ሚና ተወጥቷል።
አዶልፍ ኤክማን ለብዙሃን ሰቆቃ መንስኤ ሆኖ ከከረመ በኋላ በጦርነቱ ማብቂያ ላይ ራሱን ቀይሮ ተሰደደ። ወደ አርጀንቲና ቦነስአይረስ አቅንቶ ሌላ ሰው ሆኖ መኖር ጀመረ።
ወደ አርጀንቲ ካቀና 14 አመት በኋላ ሪካርዶ ክሌመንት የሚባል ጎልማሳ በሞሳድ እጅ ወደቀ። የሞሳድ መሪማሪ 'አንተ ማነህ' ቢለው ጎልማሳው 'ክሌመንት ነኝ' አለ። 'አዶልፍ ኤክማን መሆንህን ደርሰንበታል' ቢባል 'በፍፁም አይደለሁም' ብሎ ሞገተ።
መርማሪው የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ ከቆየ በኋላ ድንገት ''የና.ዚ አባል ሳለህ የSs ቁጥርህ ስንት ነበር?'' ብሎ ሲጠይቅ ክሌመንት ሳያስበው ቁጥሩን ተናገረ። ሁሉም ነገር እዚህጋ አበቃ። ሳያስተውል ማንነቱን አጋለጠ።
ለአመታት ስሙን ቀይሮ በአርጀንቲና የከረመው ስሙን ሪካርዶ ክሌመንት ብሎት የበረው ጎልመሳ አዶልፍ አኬማን መሆኑ ተረጋገጠ። የሞሳድ ሰዎች የኤክማንን ጉሮወው ይዘው ወደ እስራኤል መዲና ወሰዱት፥ ሞሳዶች ግዳይ ጣሉ።
አዶልፍ ኤክማን፥ በሰራቸው ወንጀሎች ሁሉ ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋግጦ በስቅላት እንዲገደል ተፈረደበት
መገደሉ ቁርጥ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ወደ መስቀያው አቅንቶ እንዲህ ተናገረ
"ጀርመን ለዘላለም ትኑር ፥ አርጀንቲና ለዘላለም ትኑር ፥ ኦስትሪያ ለፈላለም ትኑር። ወደጆቼን አመሰግናለሁ ፥ በእግዚአብሔር ታምኜ እሞታለሁ"
ከዚህ በኋላ ተገደለ
@Tfanos
አዲስአበባ ፥ መብት አልባ ከተማ
* * *
በአንድ ሐገር ውስጥ ለአንዱ ቡድን መብት ሰጥቶ ለሌላው መገደብ ግልፅ አድሏዊነት መሆኑን ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው። በሚያስገርም ሁኔታ አዲስ አበባ እና አዲስ አበቤ በሕግ ጭምር የመብት ገደብ ተጥሎባቸዋል።
የሕግ ገደቡ ሳያንስ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ አዲስ አበቤን መገፍተር እና ማሳነስ 'የፌደራሊዝም' መገለጫ መስሏል።
ሕገመንግቱ ለአዲስ አበቤ ከነፈጋቸው መብቶች ጥቂቶቹን እንመልከት
የሕገመንግስቱ አንቀፅ 47 የፌደራል መንግስቱ አካላት ማንነትን የሚያብራራ ሲሆን ክልሎች "ብቻ" የፌደራሉ መንግስት አባላት መሆናቸውን ደንግጓል። ሁሉም ሰው እንደሚገነዘበው አዲስ አበባ ክልል አይደለችም። በዚህ ግልፅ ድንጋጌ መሰት አዲስ አበባ የፌደራሉ መንግስት አካል/አባል/ አይደለችም።
ምናልባት "አዲስ አበባ ለወደፊቱ ክልል ሆና የፌደራል መንግስት አካልነትን እድል ታገኛለች" የሚል ቅን ሰው ቢኖር ሕገመንግስቱ በ አንቀፅ47 ቁጥር 2 ላይ በግልፅ የአዲስ አበባ ክልል የመሆን መብት ላይ ገደብን አኑሯል። በሕገመንግስቱ መሰረት ክልል የመሆን መብት የተሰጣቸው በዘጠኙ ክልሎች ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ብቻ ናቸው።
አዲስ አበባ ብዙ ሚሊዮን ዜጎችን ያቀፈች ብትሆንም የፌደራል መንግስት አካል እንዳትሆን በመንግሥት የተፈረደባት ናት
ሕገመንግስቱ አንቀፅ 61 ስለፌደሬሽን ምክር ቤት ያወራል።
አንቀፅ 61 ቁጥር 1ን መሰረት አድርገን የአዲስ አበቤን ጉዳይ ብንገመግም አዲስ አበቤ ውክልና አልባ ሆኗል።
"የፌደሬሽን ምክር ቤት በፌደራሉ መንግስት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔሮች ፥ ብሔረሰቦች ፥ ህዝቦች በሚልኳቸው አካላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው" ይላል
በዚህ መሰረት አድስ አበባ እና ነዋሪዎቿ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውክልና እንዳይኖራቸው በሕገመንግስቱ ተከልክለዋል
የሕገመንግስቱ 62ኛ አንቀፅ የፌደሬሽን ምክር ቤት ስልጣን ምን እንደሆነ ያትታል።
በዚህ መሰረት ፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገመንግሥት መተርጎም ፥ የራስን እድል በራስ መወሰን ፥ የሕገመንግስት አጣሪ ጉባኤ ማደራጀት ፥ የበጀት ድጎማ ቀመር ማበጀት ወዘተ ሚና አለው። አዲስ አበባ በዚህ ጉዳይ ውክልና አልባ ናት።
አዲስ አበባ ርዕሰ መዲና ከመሆኗ በተጨማሪ ከፍተኛ የተማረ የሰው ሃይል ያቀፈች ከፍተኛ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የያዘች ከተማ ብትሆንም የከተማው ህዝብ በሕገመንግስቱ የመብት ገደብ ተጥሎበታል።
እንደ ሀረሪ ያሉ ከአዲስ አበባ አንፃር ጥቂት ህዝብ የያዙ ክልሎች የተሰጣቸው መብት ለአዲስአበባ ነዋሪ ተነፍጓል።
ለምን ?
@Tfanos
መንግስት እና የህዝብ አስተዳደር
* * *
'ልደቱ አያሌውን በየቦታው አትጥቀሰው' የሚል ወቀሳ እንዳታነሰቡኝ ፈርቼ ይህን ፅሁፍ ልደቱ በሰጠው አድናቆት ከመጀመር ወደኋላ አልልም 😂😂
ልደቱ አያሌው 'መድሎት' በሚለው መፅሐፉ "ባለፉት መቶ አመታት እንደነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ያለ አሰላሳይ አልተፈጠረም" በማለት ነጋድራስን አወዳድሷል። ሃብታሙ አለባቸው 'ታላቁ ተቃርኖ' የሚለውን መፅሐፉ ለነጋድራስ ገብረህይወት መታሰቢያ አውሎታል።
ነጋድራስ ገብረህይወት በ1911 ሲሞት እድሜው ገና 31 ነበር። ነገር ግን ከመሞቱ በፊት ያበረከታቸው ሁለት መፅሐፍት ከወጣት አእምሮ የፈለቁ አይመስሉም። ምክሮቹ ዛሬም ድረስ የሚያገለግሉ ፥ ትንታኔዎቹ ዘመንን ተሻግረው የኛንም ዘመን የሚዋጁ ናቸው።
ገብረህይወት ባይከዳኝ 'አጤ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ' እንደመሁም 'መንግስት እና የህዝብ አስተዳደር' የሚሉ ሁለት መፅሐፍት ያበረከተ ሲሆን በስራዎቹ ታሪክ ፥ ፖለቲካ ፥ ኢኮኖሚ ፥ አስተዳደር ወዘተ በስፋት ተነስተዋል።
መፅሐፎቹ መቶ አመትን የተሻገሩ ሲሆኑ የሰውዬውን አርቆ አሳቢነት ለመገንዘብ እንዲረዳዬ በጣም ጥቂት ሃሳቦችን አንስተን እንመልከትና የአስተሳሰቡን ጥልቀት እንመስከር
አጤ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ ከሚለው መፅሐፍ እንጀምር
በገፅ 19፥ ዛሬም ድረስ ህመማችን የሆነውንና ለኋላ መቅታችኝ እርሾ ያኖረዎውን የመከፋፈል ልክፍት አሳሳቢነት ገልጿል።
"እኛ ኢትዮጵያውያን ካለመስማማታችን የተነሳ ሌሎች ህዝቦች በአእምሮና በጥበብ እየበረቱ ሲሄዱ እኛ ወደ ኋላ ቀረን " ገፅ 19
በገፅ 28 ስለ ሃይማኖት ነፃነት ያሳሰበ ሲሆን መንግስት ሃይማኖትን ለሃይማኖተኞች እንዲተው ዳኝነቱም የፈጣሪ እንጂ የንጉስ እንዳልሆነ አሳስቧል።
(የሃይማኖት መብትና ሴኩላሪዝምን የሚመለከት ብርሃን ለማብራት ጥሯል) የግብር ስርኣት እንዲሻሻል ፥ ዘመናዊ ሕገመንግሥት እንዲወጣ ፥ የሃይማኖት አርነት እንዲታወጅ ፥ እንቅስቃሴ የሚያውክ ኬላ እንዲቀንስ ወዘተ መክሯል።
ከሁሉም በላይ የመንግስት እና የንጉስ ሃብት እንዲለያይ አበክሮ አሳስቦ ነበር። መፅሐፉ በዘመነ ኢያሱ የተፃፈ ሲሆን በሚያሳዝን ሁኔታ ዛሬም ድረስ የነጋድራስ ምክር አልተተገበረም። ፓርቲ እና መንግስት መካከል ግልፅ መስመር አልተበጀም።
"መንግስት እና የህዝብ አስተዳደር" ይሄ ሁለተኛው የነጋድራስ መፅሐፍ ሲሆን እጅግ ጥልቅ በሆኑ ሃሳቦች የታጨቀ መፅሐፍ ነው።
በተለይ የትምህርትን ጉዳይ ደጋግሞ አሳስቦበታል። 'መንግስት አውራ ጥረቱ ትምህርትን ማስፋፋት' ነው ይላል። እውቀት የነፃነት እና የሃብት ምንጭ መሆኑን ገልጿል። መንግስታት ሃይል ስላላቸው ብቻ መግዛት እንደማይችሉ ይልቁንም ስራቸው በእውቀት መሰረት እንዲቆም ወትውቷል።
በመፅሐፉ የሚገርሙኝ ሁለት ነጥቦች ናቸው።
የመጀመሪያው ስለ ሐገር ፍቅር ያነሳው ነው። ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎታቸው ካልተሟላ ለሐገራቸው ያለ ፍቅር እና ታማኝነት እየተሸረሸረ ስለሚሄድ ዜጎችን ከድህነት የሚያወጣ ፖሊሲ የሀገር ፍቅርን መገንቢያ መሳሪያ መሆኑን ከመቶ አመት በፊት አሳስቦ ነበር።
ሌላው ፥ ስለ ሕግ እና ስርኣት የፃፈው ነው። ሹማምንት አንድ መመሪያ ከራሳቸው ልብ እና ፈቃድ አውጥተው ቢተገብሩ የረባ ውጤትን ማምጣት አይችሉም። ይልቅ የትኛውም የመንግስት እቅድ አስቀድሞ ከህዝብ ስነልቦና ፥ ፍላጎት ፥ ሁኔታ ባህል ጋር የተሰናሰለ እንዲሆን በብርቱ መክሮ ነበር። ይህ ምክር ዛሬም ድረስ ለፖሊሲ አውጭዎች ሊሰጥ የሚገባ ምክር ነው።
(በነገራችን ላይ የስልኬ ዌልፔፐር የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ፎቶ ነው
@Tfanos
አንዳንድ አክራሪ ብሔርተኞች ኢትዮጵያ ብትፈርስ ከነሱ በተፃራሪ የቆመ አካል ተለይቶ የሚጎዳ ይመስላቸዋል። (ብዙ ብሔርተኞች ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የተቃራኒዎቻቸው ጉዳት ፍስሃ ይሰጣቸዋል። የፖለቲካ ስሌታቸውም ከዚህ ይመነጫል)
ኢትዮጵያ ብትፈርስ ተለይቶ የሚጠቀም ወይም ተለይቶ የሚጎዳ የለም። ከኢትዮጵያ ፍርስራሽ ሐገር እሰራለሁ የሚል ብሔርተኛ ካለ የለየለት ጂ.ል ነው።
የሚበጀው አጓጉል መጎተቱን ትቶ ፥ ሳይረፍድ በፊት ስለጋራ ጥቅም መዋያየት ነው።
@Tfanos
በድሬዳዋ የምትገኘው መካነየሱስ ቤተክርስቲያን አጥቢያ 'በአንድ ወር ጊዜ ከዚህ ልቀቂ' ተብላለች።
ቦታው በሕግ እውቅና የተሰጠው የመካነ-ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ንብረት ቢሆንም በቤተክርስቲያን ሕጋዊ ይዞታ ላይ ሆቴል እንዲሰራ በተማው ሹማምንት ተወስኗል።
ይህ መንግስት ከሕግ በላይ ነው፥ ሐይማኖት ተቋማት አይከበሩም፥ሹማምንት እንዳሻቸው መወሰን ይቻላሉ። ያሳፍራል
@Tfanos
የግዜ ጉዳይ እንጂ ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ውጊያ የሚቀር አይደለም።
ወለጋ በከበባ ውስጥ ነው፥ ትግራይ ቁስሏ አልሻረም፥ አማራ ጦርነት ታውጆበታል፥ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ወቅት እየጠበቀ በሚያገረሽ ግጭት ደም ይፈሳል፥ ሶማሌ በአልሸባብ ይታመሳል፥ አፋር የጦርነቱ ጠበሳ አልዳነለትም፥ ደቡብ ውስጥ ግጭቶች አሉ።
ይህ ሁሉ ሞት ስለማይበቃ ለተጨማሪ ሞት ለመዋጋት እያሟሟቅን ነው።
ማዳበሪያ ለመግዛት ፥ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት ፥ ለሰራተኞች ደሞዝ ለመክፈል ፥ ወዘተ ገንዘብ የለም። ጥይት ለመግዛት ግን በቂ ገንዘብ አለን።
መንግስትን የሚተቹ ከትላንት በስቲያ 'ለውጥ የመጣባቸው' ትላንት 'የጁንታ ተላላኪ' ይባሉ ነበር። ዛሬ ደግሞ 'ጃዊሳ' የሚል ታርጋ ይለጠፋል። ለነገ ደግሞ 'የሻቢያ ተላላኪ' የሚል ታፔላ ተዘጋጅቷል።
በአንድ እንቅፋት ደጋግሞ መመታት ሆኗል የኛ እጣ !
@Tfanos
ሰውዬው ክፍል አራት
* * *
አንዳንድ ጊዜ ከአንዳንድ ወንዶች ጋር ፆታ መለዋወጥ ያምረኛል፡፡ ለአንድ ቀን ብቻ ፆታ ተቀያይረን የሚሰማኝ ስሜት ቢሰማቸው ብዬ እመኛለሁ፡፡
አንዳንድ ወንድ ገንዘብ ስላለው ብቻ ካልሲ ካልሲ በሚል አፉ ሊስመኝ ሲታገል 'ምናለ ቦታ ተቀያይረን የሚሰማኝ ስሜት በተሰማው?' እላለው፡፡
ብብቱ የሚከረፋ ወንድ በእቅፉ ሆኜ እንድስቅለት ሲፈልግ 'አሻፈረኝ' ስለው የከፈለውን ገንዘብ ማስላት ሲያሰኘው ቦታ መቀያየር ያምረኛል፡፡
ሴተኛ አዳሪ መዋሰቢያ አካል እንጂ አእምሮ ያላት የማይመስለው ደደብ ሲያጋጥመኝም ተመሳሳይ ስሜት ይሰማኛል፡፡
ተገዶ መደፈር የሚፈጥረውን ምርቅዝ ቁስል ባሰብኩ ቁጥር ከደፋሪዎች ጋር ፆታ ተቀያይሬ ህመሜን እንዲታመሙ ማድረግ ብችል ብዬ እመኛለሁ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ከአንዳንድ ወንዶች ጋር ፆታ መቀያየርን እመኛለሁ፡፡ የትኛውም ወንድ የሚሰማኝ ስሜት ሊገባው እንደማይችል ራሴን አሳምኜ ነበር።....በጊዜ ሂደት በቃላት ሊነገር የማይችል የውስጥ ህመሜን ሊገነዘብ የሚችል አንድም ሰው እንደማይኖር ለራሴ ነግሬ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ 'ውስጤን መረዳት የሚችል አንድ ሰው አለ ማለት ነው' አልኩ፡፡ 'ፆታዬን ሳልቀይረው ህመሜን የሚረዳ አንድ የተለየ ወንድ አለ' ብሎ ማሰቡ እርካታን ፈጠረብኝ፡፡
"ታውቃለህ" አልኩት ስለራሴ ባወራውለት ቁጥር የሚሰማኝ ደስታ እየጨመረ፡፡
"ታውቃለህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወንድ ልጅ ጋር ሳድር የተከፈለኝ መቶ ብር ብቻ ነበር፡፡ ያን ክርፋታም ገላውን ላቀፍኩበት ጋን ጋን በሚል አፉ ሊስመኝ ለታገለበት ደግሞም የመጀመሪያውን ዙር ከጨረሰ በኋላ ሊደግም ሲል 'ትንሽ እንረፍ' ስለው 'የከፈልኩት እኮ በየ ስንት ደቂቃ ልዩነት ማድረግ እንዳለብኝ እንድትነግሪኝ አይደለም' ብሎ ላሸማቀቀኝ ሲያንቀላፋ ደግሞ እንደተበላሸ መኪና ላንኮራፋበት በየደቂቃው ግማታም ፈሱን ለፈሳበት ሁሉ የከፈለኝ መቶ ብር ነው፡፡ መቶ ብር ብቻ!.... ከዛ ግም ሰው ጋር ካደርኩ በኋላ ራሴን ይበልጥ ናቅሁ፡፡ በሂደት ደግሞ ይበልጥ የምናቅ ሴት ሆንኩኝ፡፡
..ዛሬ ላይ የተነጠቅሁትን ህልሜን ማስመለስ አልችልም፡፡ የተዘረፍኩትን ብሩህ ቀን የአበባነት እድምዬን የተቀማሁትን ጨዋነቴን ወዘተ ማስመለስ አልችልም፡፡ የተወሰደብኝን እምነት ማስመለስ አልችልም፡፡ እኔ ማንነቴን ተዘርፌያለሁ እድሜዬን ተነጥቄያለሁ ህልሜ ተወስዶብኛል ጨዋነቴን ተቀምቻለው ሴትነቴ ከስሟል፡፡ ... ታውቃለህ ሰባት ጊዜ አስወርጃለው፡፡ ሰባት ጊዜ! ለመጨረሻ ጊዜ ሳስወርድ ሃኪሙ ምን እንዳለኝ ታውቃለህ? 'በተደጋጋሚ በማስወረድሽ የተነሳ ከዚህ በኋላ ማህፀንሽ ልጅ መሸከም አይችልም' ነበር ያለኝ፡፡ ሃኪሙ እንዲህ ሲለኝ በወቅቱ ምንም አልተሰማኝም ነበር፡፡ 'ማንነቷን ለተነጠቀች ሴት ልጅ ምኗ ነው?' አልኩኝ በልቤ፡፡ 'ሴትነቴን ከተነጠቅሁ በኋላ ምን ላደርግ እወልዳለው?' ብዬም ነበር፡፡ ነገር ግን ከቀናት በኋላ ነገሩ ይጠዘጥዘኝ ጀመር፡፡ የመውለድ ፍላጎት ተፈጠረብኝ እናት የመሆን ጉጉት አደረብኝ፡፡ ግን ምን ያደርጋል ባዶ ህልም!"
ሲያዳምጠኝ ከቆየ በኋላ ያለመታከት የሚወርደውን እንባውን እየጠረገ
"ከዛ በኋላ ራስሽን ለማጥፋት ወሰንሽ አይደል?" ሲለኝ ግራ በመጋባት ስሜት አየሁት፡፡
"ግራ አትጋቢ የነገርሽኝን ታሪክ በሙሉ አውቅ ነበር፡፡ ያልነገሽኝንም ታሪክሽን አውቃለሁ፡፡ አንቺ የማታውቂውን ታሪክሽንም አውቃለሁ ስለራስሽ እንድትነግሪኝ የፈለግሁት አንቺ ራስሽን ለእኔ የማሳየት ፍቃደኝነት እንዲኖርሽ ነው" አለኝ ተረጋግቶ
"አንተ ማነህ" አልኩኝ ይበልጥ ግራ ተጋብቼ
(የመጨረሻው ክፍል ነገ
@Tfanos