ለአጫጮር ልብወለዶች ስብስብ አጠር ያለ ማስታወቂያ
"ነገን ፍለጋ" ያልናት መፅሐፋችን የካቲት 27 በአዲስ አበባ ወመዘክር ትመረቃለች።
ዝግጁ?
ለእናቴ ቀሚስ ገዛሁላት። ከዛ ለ 9 ሚሊዮን 7 መቶ 89 ሺ 654 ሰው ደውላ ፥ ቤታቸው ሄዳ ፥ ቡና አፍልታ ወዘተ ቀሚስ እንደገዛሁላት ነገራቻቸው።
በቅርቡ ለአለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ትሰጣለች ብዬ እጠብቃለሁ።
በውነቱ ወይዘሮ ምህረት ትለያለች
@Tfanos
"መልካሙ ይባላል፥ ጓደኛዬ ነው። የስልክ ባለሞያ ነው። ያው ስልክህ ከተበላሸ እሱ ይሰራልሃል"
"ጌች ይባላል። ባነር ፥ ግራፊክስ ፥ የመፅሐፍ ሌይ አውት ወዘተ ይሰራል። ጓደኛዬ ነው"
"ዜና ትባላለች። ጋዜጠኛ ናት። አሁን ብሮድ ካስት ባለስልጣን ነው የምትሰራው። ዜና ስታነብ ፥ ስትተርክ ፥ ወዘተ ድምጿ እንዴት እንደሚያምር"
ምን ለማለት ነው?
ጓደኞቻችሁን በዚህ መንገድ አስተዋውቁ። ስማቸውን ብቻ ሳይሆን ስራቸውን ጭምር መግለፅ ይጠቅማቸው ይሆናል።
@Tfanos
"ሀዲስ አለማየሁ ፥ ዲፕሎማቱ ደራሲ"
* * *
በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 1958 አ.ም ኢትዮጲያዊው ታላቅ ደራሲ ሃዲስ አለማየሁ "ለአለም መንግስታት የማቀርበው ማሳሰቢያ አለኝ" አለ።ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኒውክለር ቦንብ እና ኬሚካል መሳሪያዎችን የሚመለከት አቤቱታ ሃዲስ አቀረበ። "እኚህ የጦር መሳሪያዎች ጅምላ ፈጅ ስለሆኑ አጋጅ ሕግ ይውጣ" አለ። ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎችን የሚያግድ ጥያቄ በማቅረብ የመጀመሪያው ሰው ሃዲስ አለማየሁ ሆኖ ተመዘገበ።
ደራሲ ሃዲስ አለማየሁ በወቅቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ነበር። የሐገራችን ዲፕሎማት የነበረው ሀዲስ ሃሳቡን አርቅቆ እና አደራጅቶ ለተመድ አቀረበ።
"አለም የኒውክለር ቦንብን እንዲሁም የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን እንዳትሰራ እና እንዳትጠቀም በሕግ ይታገድ" የሚል ሰነድ በሀዲስ በኩል ተዘጋጀ።
እንግሊዝ ፥ ፈረንሳይ እና አሜሪካ በሃዲስ ሃሳብ ተደናገጡ። ነገሩ አሳሰባቸው። ሃሳቡ በመርህ ደረጃ ልክ እንደሆነ ቢታወቅም ታላላቆቹ ሐገራት ጥቅማቸው ለአደጋ እንደሚዳረግ ስላመኑ ሀዲስ አለማየሁን "ሃሳብህን ከመድረክ አንሳው (ዊዝድሮው አድርግ)" ብለው ጠየቁ።ሃዲስ ግን አሻፈረኝ አለ።
ትልልቆቹ ሐገራት ያላቸውን ድምፅ እና የዲፕሎማቲክ አቅም በመጠቀም በቀላሉ የሃዲስን ሃሳብ መጣል ቢችሉም ይህ ለፖለቲካ ታሪካቸው ጥቁር ነጥብ ስለሚፈጠር መጠንቀቀ ፈልገዋል። ስለዚህ ሀዲስ አለማየሁን "ግድ የለህም፥ ሃሳብህን ተወው" አሉት።
* * *
ሀዲስ አለማየሁ አርበኛ ጭምር ነበር። ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረች ግዜ "የአባቶቼ ግዛት አይደፈርም፥ በህይወት እያለሁ ሐገሬን ጠ.ላት አይገዛትም" ብሎ ነፍጥ ታጥቆ ፥ ጎራዴ አንግቦ ዱር ወረዷል። ከአርበኞች ጋር በዱር በገደሉ ከፋ.ሽስት ጋር ሲፋለም ከረመ። (የአርበኝነት ታሪኩን "ትዝታ" በሚለው መፅሐፉ ማንበብ ትችላላችሁ)
ጣሊያን ኢትዮጲያ ላይ የመ.ርዝ ጋዝ በመጠቀም ያደረሰችውን ጉዳት በአይኑ በብሌኑ ተመልክቷል። ኢትዮጵያዉያን ለአሰቃቂ ሞት እና ለዘግናኝ ስቃይ መዳረጋቸውን አይቶ ልቡ አዝኖ ነበር።
ከአመታት በኋላ ዲፕሎማት ሲሆን "በእኔ ሐገር ህዝብ ላይ የደረሰ መከራ በሌላው ህዝብ ላይ እንዲደገም ስለማልፈልግ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን የሚያግድ ሕግ ይውጣ" በማለት ለአለም መንግስታት አቤት አለ። የአሜሪካን ተግሳጽ ፥ የእንግሊዝን ግልምጫ ፥ የፈረንሳይን ምልጃ ችላ ብሎ በአቋሙ ፀና።
ትልልቆቹ ሐጠራት ሐዲስ አለማየሁን ማሳመን እንደማይቻላቸው ሲያምኑ ወደ አዲስ አበባ ስልክ መቱ። ለንጉሰ ነገስቱ አሳሰቡ።
አፄ ሃይለስላሴ ሀዲስን አዘዙት። "ነገሩን ተወው" አሉት።
ሀዲስ ያኔ "ጥያቄዬን ዊዝድሮው አላደርግም። ነገር ግን ከንጉስ ቃል ወጥቼ ልገፋበትም አልፈልግም። ጥያቄዬ በሪኮርድ ፋይል ሆኖ ይቀመጥልኝ" አለ። እንዳለው ተደረገለት።
ዛሬ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ አለም የሃዲስ አለማየሁን ስጋት የምትሰጋበት ዘመን ሆኗል። ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች አሳሳቢ ሆነዋል። ደራሲ ሃዲስ አለማየሁ ግን አስቀድሞ ጆሮ የተነፈገ ማስጠንቀቂያ አሰምቶ ነበር።
@Tfanos
እንኳን አደረሳችሁ ፥ እንኳን አደረሰን።
በነገው እለት ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ሲባል የተወለድኩበት ቀን መታሰቢያ በመላው ኢትዮጵያ በደማቅ ስነስርዓት ይከበራል።
ልደቴን ምክኒያት በማድረግ አልኮል አለአግባብ አትጠጡ፥ ከጠጣችሁ አትንዱ።
ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲባል የተወለድኩበትን ቀን መታሰቢያ የተቸገሩትን በመርዳት ፥ ያላችሁን በመካፈል ፥ እርስ በእርስ በመተጋገዝ አክብሩት።
(ለኔ መፅሐፍ ስጥታ መስጠቱ አይረሳ)
በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ
የግል መኪኖች ላይ የሰአት ገደብ ሊጣል ነው። የዚህ ምክኒያቱ በጣም ያስቃል።
ፀሐዩ መንግስታችን የቤት ውድነትን ለመቀነስ "አከራዮች የቤት ክራይ አትጨምሩ" የሚል አስቂኝ መፍትሄ ሲሰጥ ነበር።
መንግስት በፈለገበት ሰአት የመብራት ፥የውሃ ፥ የግብር ጭማሪ ያደርጋል። ዜጎች ለኮንዶሚኒየም ማሰሪያ ቆጥበው ሲያበቁ ቤት በመስጠት ፈንታ 'የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ' አይነት ሰበብ ያቀርባል።
"ሞተር ሳይክል በመጠቀም ወንጀል የሚሰሩ ሰዎች ስላሉ ሞተር ሳይክል መንዳት አግጃለሁ" ስል የማያፍር መንግስት ነው ያለን።
አመራሮቻችን በፈለጉበት ወቅት የንብረት ዝውውር እግድ ይጥላሉ።
ሰዎች በገዛ ንብረታቸው የማዘዝ መብት የማይኖራቸው ለምንድነው?
የገዛ ንብረት ላይ የማዘዝ መብትን መቀማት ምን አይነት ትርጉም እንዳለው የማይገባቸው ለምንድነው?
"ደሃ ተኮር ካፒታሊስት ነኝ" የሚል ግራ አጋቢ ፖሊሲ አራማጁ መንግስታችን ከደርግ ስህተት የማይማረው ለምንድነው?
ውሃ ቀጠነ እያሉ መብት ላይ ገደብ መጣል ፥ የዜጎችን ንብረት ለመቆጣጠር መሞከር የረባ ውጤት እንደማያመጣ የደርግ መንግስት ምስክር አይሆንም?
ፖሊሲ አውጪዎቻችን ፥ ደንብ አርቃቂዎቻችን አማካይ የግንዛቤ ደረጃ ያለው ሰው የማይስተው እየሳቱ የሚቀጥሉት እስከመች ነው?
@Tfanos
"ፍርዳችሁ እስር ቢሆንም መሞት አለባችሁ"
* * *
ጓድ መንግስቱ ሃይለማርያም ሐገር አማን ብለው ለስራ ጉብኝት ባቀኑበት ወቅት ድንገተኛ ነገር ተከሰተ። የጦር ጀነራሎች መንግስቱ ሃይለማርያምን ከመንበር ሊያወርዱ የመፈንቅለ መንግስት እንቅስቃሴ ጀመሩ።
የደርግ መንግስት በኤርትራ ከሻበያ ጋር በትግራይ ደግሞ ከወያኔ ጋር ሲያደርግ የነበረው የተራዘመ ጦርነት የወታደሩን ህይወት እንደዋዛ ቢያስከፍልም ከድል ይልቅ ሽንፈትን ፥ ከስኬት በላይ ውድቀትን አስከተለ። የደሃ ልጆች በውድ እና በግድ ወደ ጦር ግንባር እየተላኩ ደመ-ከልብ ሆኑ።
ወጣቶች ከእናታቸው አጠገብ ተወስደው በወጡበት ቀሩ። እናቶች ልጃቸውን አጡ፥ ሴቶች ባል አልባ ሆኑ፥ አባቶች ጧሪያቸውን ተቀሙ፥ አንዳንዶች የወልዷቸውን በወጉ ሳያቅፉ የጦርነት እሳት በላቸው።
መንግስቱ ሃይለማርያም ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ አለመፈለጋቸው ፥ በግትርነታቸው የተነሳ ድርድርን ማበላሸታቸው ፥ ከጦር ሜዳ ውድቀት በኋላ እንደ ቀልድ የሰራዊቱን አመራሮች ማስረሸናቸው ያበሳጫቸው ጀነራሎች "መንግስቱ ከዚህ በኋላ ይበቃዋል" ብለው ወርሃ ግንቦት 1981 አ.ም መፈንቅለ መንግስት ሞከሩ። ነገር ግን እቅዳቸው አልሰመረም። መንግስቱ ሃይለማሪያምን የመፈንቀል ሙከራቸው ከሸፈ።
የፋሲካ ሲደልልን "የሻሞላው ትውልድ" መፅሐፍ ምስክር ጠርተን መፈንቅለ መንግስት ጠንሳሾቹ ላይ የተወሰደውን እርምጃ እናውሳ።
የመንግስት ግልበጣ ጠንሳሾች ከተያዙ በኋላ የደርግ መንግስት ሕግ ያልተከለ የበቀል እርምጃ እንዳይወስድ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተማፅኖ አሰሙ። ጓድ መንግስቱ ሃይለማርያም "ሕግ እንከተላለን እንጂ ተራ በቀል ውስጥ አንገባም" ብሎ ቃል ቢገቡም ቃሉ ታጠፈ። የጦር ፍርድ ቤቱን አስገድደው ወደ በቀል እርምጃ ገቡ።
ከደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ፋሲካ ሲደልል በመፅሐፉ እንዳሰፈረው ፥ ጉዳዩን የመረመሩት ዳኞች መፈንቅለ መንግስት ጠንሳሾች ቅጣታቸው በእስራት እንዲሆን በየኑ። በዚህም መሰረት ከፍተኛው ቅጣት 15 አመት ሲሆን ሌሎች ከ2 አመት እስከ 10 አመት እንዲታሰሩ ተስማሙ። ነገር ግን ከብይን ቀን በፊት መንግስቱ ሃይለማርያም የታሰበውን የቅጣት ውሳኔ ምንነት ጠይቀው ደረሱበት። ይሄኔ አራስ ነበር ሆኑ።
"ይሄ ቅጣት አይደለም፥ እናንተም ከነሱጋ ስትዶልቱ ነበሩ" ብሎ ደነፉ። በአስፈሪ ቁጣቸው ቅጣቱን አስለወጡ። ዳኞቹ የወሰኑትን እስር በማይገሰስ ስልጣናቸው ወደ ሞት ለወጡት። "ሞት ፍረዱባቸው" የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡ። የማይታጠፍ ትዕዛዝ!
የፍርዱ ቀን ሰብሳቢ ዳኛ እያለቀሱ ብይኑን ለተከሳሾች አነበቡ። "ሞት ተፈርዶባችኋል" አሉ ከእንባቸው እየታሉ።
በውሳኔው መሰረት ግድያው ተፈፀመ።
@Tfanos
መርዶ
* * *
"ትርሃስ ደህና ናት?"
"ሞተች እኮ"
"ምን ገጠማት?"
"መድሃኒት አጥታ"
"የማነ እንዴት ነው?"
"ተሰውቷል"
"ሐጎስስ?"
"ሚስቱ እና ልጁ በመደፈራቸው እራሱን አጠፋ"
"ምነው ሞት ብቻ ሆነ የምትነግሪኝ"
"መልአከ ሞት ጨከነብና"
"እግዚአብሔር ያፅናናሽ"
"የኔን ነገር ተይው። ይልቅ አንቺ ደህና ነሽ?"
"ደህናማ አይደለሁም"
"ዴምለው እንዴት ነው?"
"ፈንጂ ገደለው"
"ትንሹ ወንድምሽስ አደገ?"
"ወዴት ይደግ? ጥይት በላው"
"ጎንደር ያለው አጎትሽ ዳምጤስ?"
"ልጁ በጦርነት ከሞተ በኋላ በብስጭት የአልጋ ቁራኛ ሆነ እኮ"
"ምነው መርዶ ብቻ የምትነግሪኝ?"
"መልካም ዜና ከየት ላምጣ?"
@Tfanos
አጤ ሚኒሊክን ማን ገደለ?
* * *
ባለ ግርማ ንጉስ ፥ ስኬታማ የጦር አለቃ ፥ የተከበሩ መሪ ፥ የሚወደዱ አዛዥ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሞቱ። እኒያ ሳርና ቅጠሉን የሚያዙ የመሰሉት ፥ ከሹማምንት እስከ ተርታ ዜጎች ድረስ የሚከበሩ ፥ ከመሳፍንት እስከ መኳንንት ድረስ የተፈሩ፥ በውጭ ዜጎች የተደነቁ ፥ የአድዋ አርበኛ ፥ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች ታላቁ ሰው ሞቱ።
ሚኒሊክ እስከወዲያኛው ማሸለባቸውን ተከትሎ የተለያዩ ሃሜታዎች አየሩን ተቆጣጠሩት። ጃንሆይ ተመ.ርዘው እንደተ.ገደሉ ተወራ።
በእርግጥ ሚኒሊክን ማን ገደ.ለ?
አልሃንድሮ ዴል ባዩ በዘመነ ፋሽ.ስት ወ.ረራ "ለአቢሲኒያ ነብሴን እሰጣለሁ" በማለት ከአርበኞች ጋር አብሮ ለመዝመት ወደ ኢትዮጵያ መጣ። በኢትዮጵያ ቆይታው ነፍጥ ታጥቆ ከወ.ራሪ ጋር ተፋልሟል፥ ዱር ወርዶ ተታኩሷል። ወደ ሐገሩ ኩባ ከተመለሰ በኋላ የኢትዮጵያ ኑሮውን የሚያወሳ መፅሐፍ አሳተመ። መፅሐፉ እጅግ በርካታ መረጃዎች የታጨቁበት ሰነድ ነው።
በመፅሐፉ ከተወሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሚኒሊክ ሞት ነው። አንድ ሰው ለዴልባዩ "ሚኒሊክን የገደ.ልኩት እኔ ነኝ" በማለት ተናዘዘ። አዎ ተናዘዘ። ያ ሰው ስመ ጥሩ ራስ ሙሉጌታ ነበር።
ዴል ባዩ "ቀዩ አንበሳ" በሚለው መፅሐፍ እንዳሰፈረው ከሆነ ራስ ሙሉጌታ የሚኒሊክን ስም ሲጠሩ በስሜት ይንቀጠቀጡ ነበር።
በጦርነት መካከል ራስ ሙሉጌታ ተመተው ወደቁ። ጉዳታቸው የሚያገግም አይመስልም። ከሞትጋ ተጋጠሙ። በሞት ጣር ሳሉ ለዴልባዩ ተናዘዙ።
"በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁን ሰው የገደ.ልኩት እኔ ነኝ" አሉ ሙሉጌታ
"ሚኒሊክን የገደ.ሉት እርሶ ኖት?" አለ ዴልባዩ ግራ ገብቶት
"በመ.ርዝ ነው የገደልኳቸው። አዲስ አበባ ላይ አንድ ግሪካዊ ዶክተር መር.ዙን ሰጠኝ። .....ገዳይ ዱካው የማይገኝበት ሞት። ... በአንዲት የቡና ሲኒ ምኒሊክ ሞትን ፉት አሏት። ማንም አልጠረጠረም። 3 የረዱኝ ሰዎች አሉ። ጠንቋዮች ናቸው....."
ራስ ሙሉጌታ ለዴል ባዩ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠታቸው በፊት ዝም አሉ። ዝም ባሉበት ላይነቁ አንቀላፉ። ሞ.ቱ።
@Tfanos
የሰይፉ ሾውን እየተመለከትኩ ነበር።
ራኬብ እና ሰይፉ ስለ አስፋው ከተነጋገሩት ሁሉ የገረመኝ መኪናውን ለበጎ አድራጎት ስጦታ ለመስጠት መወሰኑ ነው።
መኪናዋ የአባቱ ማስታወሻ ናት። ደጋግሞ የሚጠራው ፥ ከአንደበቱ የማይለየው የመሸሻ ማስታወሻ። አባቱ መሸሻ ይነዳት የነበረች ልዩ ንብረት ናት መኪናዋ።
ለበጎ አድራጎት ስራ ለመስጠት የወሰነው ንብረት ብቻ አይደለም። ትዝታ ፥ የአባት ፍቅር ፥ ልዩ ማስታወሻ ፥ የወላጅ ናፍቆት ወዘተ ጭምር ነው።
እንዴት ያለ ልብ ነው ?
@Tfanos
የአፄ ቴዎድሮስ ጭካኔ
* * *
ዳግማዊ ቴዎድሮስ የሚዘከር ጀብድ ብቻ ሳይሆን ግራ አጋቢ ባህሪን የተላበሱ ንጉስ ነበሩ። ሲቆጡ አራስ ነበር ይሆናሉ፥ ሲጨክኑ ሰይጣ.ነት ይጣባቸዋል።
ስለ ቴዎድሮስ የተፃፉ መፅሐፍት ሁሉ ከጀግንነቱ እኩል አስፈሪ ጭካኔውን ይጠቅሳሉ። የቴዎድሮስ ባህሪ ተለዋዋጭ ሲሆን በተለይ ከሰአት በኋላ ሲሆን ብስጩ እና ግልፍተኛ ይሆናሉ።
ከደጆች ተድላ ጋር በተዋጉ ጊዜ ድል ቀንቷቸው 8 ሺ ምርኮኛ ያዙ። በጦርነት ድል የማረኳቸውን ወታደሮች እንጂባራ ላይ ሰብስቡ። ቀጥለው ጭንቅላታቸው እንዲቀላ አዘዙ። የምርኮኛ ራስ ሲያቆር.ጡ ሰአቱ ነጎደ፥ መሸ። ሲመሽ ትዕዛዝ ሰጡ፥ 'የቀረው ምርኮኛ ይቆጠር እና እየተጠበቀ ይደር' አሉ። በማግስቱ የተረፉትን ሰብስበው አስቆጠሩ፥ የጎደለ እንደሌለ ካረጋገጡ በኋላ ሁሉም እንዲ.ፈጁ አዘዙ።
በሬ.ሳ መሃል ሲመላለሱ አንድ ሰው ሲንፈራገጥ አዩት፥ ጣር ላይ ያለውን ራሳቸው ጨረሱት።
ከእለታት በአንዱ ማህደረ-ማሪያም የሚባል ቦታ ሲሄዱ ካህናት ልዩ አቀባበል አደረጉላቸው። ንጉሱ ግን ድንገት ያለ ሰበብ ቁጣቸው ገነፈለ። 450 ካህናትን ሰብስበው በጎራዴ አሳረ.ዱ።
ወደ ደብረታቦር ሲጓዙ ሳለ በየመንገዱ ሰዎችን ሰበሰቡ። የተሰበሰቡቱ ቁጥራቸው 7700 ነበር። እኚህን ሁሉ ሰዎች በየቤቱ አጎሩ። ቀጥሎም እሳት ለቀቁባቸው። አዎ እሳት ለቀቁባቸው።
ሰው እንደ ችቦ እየነደደ ዋለ። ሲመሽ ከመቃጠል የተረፉቱ በማግስቱ እንዲቃጠሉ ስለታሰበ እንዳያመልጡ ጥበቃ እየተደረገላቸው አደሩ።
ያን ለሊት ከባድ ዝናብ ጥሎ ነበርና ዝናብ እየደበደባቸው አደሩ።
ሲነጋ ንጉሱ መጡ። ወደመቃጠያ ቦታ እንዲታጎሩ ትዕዛዝ ተሰጠ።
ከእናቱጋ የነበረ የ5 አመት ህፃን "እንደምሽቱ ዝናብ እንዳይደበድበን ቶሎ እንግባ" አለ እናቲቱን። የተደገሰውን የምታውቅ እናት እንባን አፈሰሰች። እያለቀሰች ሳለ ቴዎድሮስ ተመለከታት።
ንጉሱ አሽከሮቹን ጠሮቶ "ምን እያለች ነው?" አለ። ነገሩት። ይሄኔ ንጉሱ አለቀሰ።
ቴዎድሮስ "ፈጣሪዬ ሆይ ለምን እንዲህ ታደርገኛለህ? እኔን ግደ.ለኝና ፍጥረትህ ይረፍ።" ብለው አለቀሱ። ቀጥሎም ለእሳት ለተዘጋጁት ምህረት አደረጉ።
(ለዚህ ፅሁፍ ማስረጃው ምንድነው የሚል ጠያቂ ካለ፥ ሁለት መፅሐፍ ምስክር አቀርባለሁ። 1፥ "የጀግንነት ሱስ በሐበሻ አድባር" 2፥ ጳውሎስ ኞኞ "አጤ ቴዎድሮስ")
@Tfanos
"ከማንም ጋር መከራከር አቁሜያለሁ። 2+2=8 ብትሉኝ እንኳ እሺ እላለሁ። አልከራከርም። አላስረደም"
"ይሄ በጣም ስህተት ነው እኮ"
"በፍፁም ስህተት አይደለም። ላብራራልህ ቆይ....."
"ለማንም አላብራራም፥ ማንንም አልከራከርም ብለህ አልነበር? አታብራራልኝ አትከራከረኝ"
"ማለት የፈለግኩት አልገባህ እኮ..."
"ውሸታም ነህ ማለት ነው። ለማንም ምንም አላብራራም አልክ አሁን ደግሞ ልታብራራልኝ ነው.... ዝም ብሎ ጥቅስ እየደረደሩ 'ይህ የህይወት መመሪያዬ ነው' ማለት ከተራ ፕሮፖጋንዳ በቀር ምን ጥቅም?"
@Tfanos
"ኢትዮጵያ ውስጥ ሐቀኛ የታሪክ ፀሐፊ የለም"
"ከሐገራችን ታሪክ ፀሐፊዎች ስንቶቹን አንብበሃል?"
"የማንንም አላነበብኩም። ግን በቃ ሐቀኛ አይደሉም"
"ሐቀኛ አለመሆናቸውን በምን አወቅክ? ካላነበብክ ውቃቢህ ነው የገለፀልህ?"
@Tfanos
አምላክ በፈረቃ
* * *
በዘመናት መሃል ፥አምላክ እያረጀ
ሌላ አምላክ ይተካል፥ ጊዜውን የዋጀ
ወቅት ሲፈራረቅ፣
ነባር አምላክ ሞቶ፥ ሌላ ይወለዳል
አዲሱ መለኮት፣
ሸምግሎ እስኪወገድ ፥ስግደት ይቀበላል
@Tfanos
ቁ.ላ የመሸለት ባህል በኢትዮጵያ
* * *
ወሲብ ተፈጥሯዊ መሆኑን ማብራራት አይጠበቅብንም። ይህ የአደባባይ ሐቅ ነው።
አንዳንዴ ተፈጥሮ ትገረሰሳለች፥ ሰዎች ከፈጣሪ የተቸረን ፀጋ ይገፈፋሉ። ከሚነጠቁ ፀጋዎች አንዱ በወሲብ መደሰት ነው።
ጥንት አለቆች ሴቶቻቸውን የሚያጫውቱ እና የሚጠብቁ ታማኝ ወንዶችን ሲፈልጉ ብልታቸውን በማኮላሸት ይሰልቧቸው ነበር። በሐገራችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በስለት የሚሰለቡ ወንዶች ነበሩ።
ስልቦች ሃላፊነቶቻቸው ብዙ ነው። ቁ.ላው የተኮላሸ ስልብ የጌታውን ሴቶች የመጠበቅ ፥ በቤት ውስጥ የማጫወት ፥ ጌታውን የማዝናናት ሃላፊነት አለበት።
ስልብ ማግኘት እንዲሁ በቀላሉ የሚሰምር አይደለም። እድለኝነት የሚጠይቅ ከባድ ትግል ይፈልጋል።
ስልቦች ብልታቸው የሚሸለተው በባለሞያ ሳይሆን በባሪ.ያ ወይም በጦረኛ ነው። የህክምና እውቀት በሌለው ሰው መራቢያ አካል በስለት ሲገዘገዝ በሚፈጠር ደም መፍሰስ ለሞት የሚዳረጉ ብዙ ናቸዎ። በቁስል መመርቀዝ ከፍተኛ ጉዳት ብሎም ሞት ይከሰታል።
አልሃንድሮ ዴል ባዩ በፋሽ.ስት ወረ.ራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፎ ለመፋለም ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ኩባዊ ሲሆን የማኮላሸት ሂደቱ ምን እንደሚመስል "ቀይ አንበሳ" በሚለው መፅሐፉ አስፍሯል።
ቀድሞ ነገር እንዲኮላሽ የሚመረጥ ልጅ ከደሃ ቤተሰብ የሚገኝ ነው። አስገራሚው ነገር አንዳንድ ቤተሰቦች ልጃቸው ስል.ብ ሆኖ እንዲያገለግል ሲመረጥ ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል።
የሚሰለ.በው ልጅ በእድሜ ትንሽ እንዲሆን ይፈለጋል። እድሜው ከ7 የማያንስ ከ12 የማይሻገር መሆን አለበት። የዚህ ምክኒያት "ለአቅመ አዳም ከደረሰ ስለወሲብ ግንዛቤ ስለሚኖረው ሃላፊነቱን በንፁህ ልብ አይወጣም" የሚል ነው። ስለዚህ አስተሳሰቡ ጭምር እንዲሰ.ለብ ገና ጨቅላ የሆነ ታዳጊ ለመኮላሸት ይመለመላል።
የምልምሉን ብላቴና ቤተሰቦች ለማስደሰት የመሸኛ ድግስ ይዘጋጃል።
ጮማ ይቆረጣል፥ ጠጅ ይጠጣል፥ ይፎከራል ይሸለላል፥ ይሰከራል።
ሜዳ ላይ ጉድጓድ ይቆፈራል። ፈርጠም ያሉ ባሮ.ች ወይም ጦረኞች ታዳጊውን ልጅ በሃይል ይይዙታል። ሌላ ሰው ደግሞ በስለት ቀደዳ ያካሂዳል። የብልት ፍሬዎቹን ተከትሎ በስለት ይገዘገዛል። ቀደዳው ከተገባደደ በኋላ ህፃኑ በተቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ እስከትኬሻው ይገባል። ከትኬሻ በታች ይቀበራል። አዎ ይቀበራል።
ይሂ ሂደት ቀላል አይደለም። ብዙዎቹ ይሞታሉ። የነገራችን ምስክር የሆነው አሊሃንድሮ ዴል ባዩ በመፅሐፉ እንደጠቀሰው ከሆነ ከመቶ አንድ ሰው ቢተርፍ ነው ይላል። 99 በመቶ የሚሆኑቱ ይሞታሉ። በህይወት የተረፉት ደግሞ ወሲብ መፈፀም የማይችሉ ስል.ብ ይሆናሉ።
ስል.ብ ማግኘት ፈተና ከመሆኑ የተነሳ ስልቦች ለሽያጭ ከቀረቡ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣሉ።
በዚህ መንገድ የተሰለቡቱ የጌታቸው ሚስት መንገድ ስትወጣ ይከተላሉ። የጌታውቸን ሴት ልጅ ያጅባሉ። ወዘተ
@Tfanos
"አቢቹ ፥ የሰላሌው ፈረሰኛ"
* * *
ከዋርካ ስር ባለች ቋጥኝ ላይ እድሜው 16 ወይም 17 የሚሆን አንድ ብላቴና በሀዘን ተቀምጧል። ሀዘን ያደቀቀው ብላቴና ነው። ማንንም ማናገር አይፈልግም።
ይህ ልጅ ከ20 ሺ በላይ የሆኑ የሰላሌ አርበኞች ከደጃዝማች አበራ ጋር በመሆን ከጣሊያን ጦር ጋር ተፋልሞ የኢትዮጲያን ድንበር ለማስከበር ወደ ጦር ግምባር ሲዘምቱ አብሮ የነበረ ሲሆን የሰላሌው ጦር በራስ ካሳ ስር ሆኖ በአንድ አውደውጊያ ድል ካደረገ በኋላ በሀዘን የተሰበረ ነው።
የወረጃርሶው ቀዳሚ ጦር ሁለት ፊት አውራሪዎችን በውጊያው ተነጠቀ። እኒያ ሁለት ሰዎች የትንሹ ልጅ ወንድሞች ነበሩ። ብላቴናው የገዛ ወንድሞቹን ከተነጠቀ በኋላ ዋርካ ስር ልቡ ተሰብሮ ተቀምጦ ወደ ውስጦ አለቀሰ።
የተቀመጠበት ዋርካ ስር አንድ ወንድሙን የቀበረ ሲሆን ለቀናት ከዛች ቦታ ሳይነሳ ይተክዛል። ስለ ሌላኛው ወንድሙ ይጨነቃል። አብረውት ከሰላሌ ወደ ጦር ግንባር የዘመቱቱ ደግሞ ለደጅ አዝማች አበራ በኦሮምኛ እና በአማርኛ እየቀላቀሉ የሁለቱን ወንድማማች ፊት አውራሪዎች ህልፈት እና የትንሹን ልጅ ሃዘን ጉዳይ የፈጠረባቸውን ጭንቀት ይናገራሉ።
ትንሹ ልጅ ኢቢቹ ነው። ሰላሌዎች "አቢቹ ደራ ደራ" እያሉ የዘፈኑለት ተዋጊ።
እነ አቢቹ ገና ከሰላሌ ሳይነሱ በፊት የጃርሶው ጦር መሪ በህመም ሲሞቱ ሁለት ልጆቹን በህብረት ጦሩን እየመሩ የኢትዮጵያን ድንበር እንዲያስከበሩ ተሾሙ። አቢቹ ደግሞ ሁለቱን ወንድሞቹን ተከትሎ ወደ ግንባር ዘመተ። ከወንድሞቹ መካከል አንዱ በደብረ አምባ ግምባር ከፋሽ.ስት ሲፋለም ከቆየ በኋላ ወደቀ። የጀግና አሟሟት ሞተ። ሌላኛው ወንድሙ ግን የት እንደደረሰ አልታወቅም። አቢቹ አንዱን ወንድሙን ቀብሮ የሌላኛውን ወንድሙን መድረሻ አጥቶ ስለ አሮጊት እናቱ ያስባል። ወደ ሰላሌ ስመለስ ምን እላታለሁ? ይላል።
አቢቹ በቀጣይ ሁለት መቶ ወጣት እንዲሰጠው ደጅ አዝማች አበራን አስፈቀደ። ቀጥሎ ወጣቶቹን ይዞ የወንድሙን አስክሬን ፍለጋ ተሰማራ። ከዛ በኋላ ለጣሊያኖች መብረቅ ሆነባቸው። ድንገተኛ ጥቃት ይሰነዝርባቸዋል። ትጥቅና ስንቃቸውን እየዘረፈ ጦሩን አደረጀ። ያኔ የአባቹን ጀብድ የሰሙ ሁሉ በሱ ስር ለመሆን በመፈለግ ይቀላቀሉት ጀመር።
በአቢቹ ስር ያለው ወጣት ጦር ቁጥር በጨመረ ቁጥር ጣሊያኖች ፍርሃት ያርዳቸው ጀመር። ከየት መጣ ሳይበል እየተከሰተ አመሰቃቀላቸው። ጦራቸውን በተነው። አሰላለፋቸውን አናጋ።
ጃንሆይ እንኳ "ይህ ትንሽ ልጅ ከኛ በላይ ጀብድ ሰርቷል" አሉለት።
ንጉሰ ነገስቱ ጭምር በተሳተፉበት የማይጮው ጦርነት አቢቹ የተለየ ተልእኮ ተቀብሎ 4 ሺ ሰራዊት አስከትሎ አስቸጋሪውን የጣሊያን ምሽግ ለመስበር ተፋለመ። በጥቁር ፈረስ ተቀምጦ በጀግንነት ሲፋለም አቢቹን ትከሻው አከባቢ ጥይት አገኘው።
አቢቹ ደሙ እየፈሰሰ በፈረሱ ጀርባ እንደ ተቀመጠ "ኢትዮጵያ ወይንም ሞት" ብሎ ወደ ፊት አለ። ሰላሌዎቹ ወታደሮች በአማርኛና በኦሮምኛ እየፎከሩ ተዋደቁ። ከነርሱ መካከል ብዙዎች የጀግና ሞት ከሞቱ በኋላ የጣሊያን ምሽግ ተሰበረ።
"አቢቹ ደራ ደራ"
@Tfanos
1፥ ኢትዮጵያ ሐይማኖታዊ አክራ.ሪነት የደህነት ስጋቷ ነው? ትልልቆቹ ሃይማኖቶች እርስ በእርስ ይጋጩ ይሆን?
2፥ ፕሮቴስታንት እና ካፒታሊዝም ምንና ምን ናቸው? ካፒታሊዝም ያልዳበረባት አፍሪካ ውስጥ ፕሮቴስታንት ምን ይገጥመዋል?
3፥ የምዕራቡ አለም "እስላማዊ ሽብ.ርተኝነት" ከሚለው ፍረጃው ጀርባ ያለው እውነተኛ ርዕዮተ አለማዊ ገፊ ምክኒያቱ ምንድነው?
4፥ አልሸባብ የቆመበት መሰረት ምንድነው? አልሸባብ እና ኢትዮጵያስ ምንና ምን ናቸው?
5፥ የኢትዮጵያ ዋነኛ የደህንነት ስጋት ምንድነው?
ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ስትፈልጉ "ጉልጥምት ኢትዮጵያ" የሚለውን የሀብታሙ አለባቸውን መፅሐፍ አንብቡ።
ሀብታሙ "ታላቁ ተቃርኖ" በሚለው ወደር አልባ መፅሐፉ "አጥንት እና ጉልጥምት" የሚል ሃሳብ ያስተዋወቀን ሲሆን ይሄን ሃሳብ ያዳበረበት መፅሐፉ ነው።
በጠጣር ሃሳቦች የታጨቀ መፅሐፍ ማንበብ የሚወድ ሰው ሀብትሽን ያንበብ።
ሁሌም እንደምለው ፥ የወለደችው እናት ትባረክ
@Tfanos
ፀሐዩ መንግስታችን "የአድዋ መታሰቢያ ሙዝዬም ሰርቻለሁ" ብሏል። በነካ እጁ ዜጎች አድዋን በነፃነት ያከብሩ ዘንድ ቢፈቅድ ትልቅ ቁምነገር እንደሰራ ይታሰብለታል።
አድዋ በደረሰ ቁጥር ከዜጎችጋ እሰጥ አገባ እየገጠሙ የአድዋ መታሰቢያ መስራት የማይታረቅ ተቃርኖ ይሆናል።
@Tfanos
"እውነት ፕሮቴስታንት ሀይማኖት የካፒታሊዝም መንፈስ ነውን?"
"..... በግዜ ሲታይ ሁለቱም የ15ኛው ክፍለ ዘመን ክስተቶች ናቸው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አንድ ላይ በቅለው አንድ ላይ አድገዋል። በቦታ ደግሞ የሁለቱም መፈጠሪያ ምዕራብ አውሮፓ ነው። በይዘት በኩል ሁለቱም ፊውዳሊዝምንና የካቶሊክ ሀይማኖትን በመቃወም እና በማመፅ የተፈጠሩ ናቸው። ሁለቱም ግለሰባዊነትንና ያልተማከለ አገዛዝን መመሪያቸው አድርገው የተነሱ ናቸው"
"ሁለቱም ነፃ ገበያን ፣ ነፃ ምርጫን ፣ ነፃ ውሳኔንና ውድድርን ያደንቃሉ፥ ይከተላሉ። ሁለቱም ቁሳዊ ሀብት ዋጋ እንዳለው ፣ ፈጠራ የፀጋ መንገድ መሆኑን ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንት ትክክል እንደሆኑ አጥብቀው ያምናሉ። ስለዚህ ካፒታሊዝም ያለ ፕሮቴስታንቲዝም አይነ-ስውር ነው። ፕሮቴስታንቲዝም ያለ ካፒታሊዝም እግር ከወርች የተፈጠረ እስረኛ ነው ይላሉ"
"... ፕሮቴስታንቲዝም ካፒታሊዝም ባልዳበረባቸው የአፍሪካ ሐገራት ችግር ገጥሞታል። የአፍሪካ ፕሮቴስታንቶች ፕሮቴስታንት በመሆናቸው ብቻ ግለሰባዊ ናቸው። ግለሰባዊነት መሪ አስተሳሰባቸው ነው። የአፍሪካ ሕዝብ ግን መሰረቱ ጋሪዮሻዊ ነው። አስተሳሰቡም ጋሪዮሻዊ ነው...."
"ፕሮቴስታንቶች አፍሪካ ውስጥ ያለ ተፈጥሯዊ ዞጋቸው መኖር አለባቸው።.... እንደ አውሮፓው ጴንጤ አዳዲስ ነገሮችንና ሃሳቦችን ማመንጨት አይችሉም። ካፒታሊዝም ስለሌለ ለመዋሀድ ማበረታቻ የላቸውም"
ከሐብታሙ አለባቸው "ጉልጥምት ኢትዮጵያ" መፅሐፍ የተወሰደ
@Tfanos
"በሚኒሊክ ስም የሚደረግ መሃላ ቅዱስ ነው"
* * *
የጣሊያን ወራ.ሪ በአድዋ አከርካሪው ከተመታ በኋላ ቂም ቋጠረ። መሸነፉ ጥርስ አስነከሰው። ለድፍን 40 አመታት የበቀል ዝግጅት ካደረገ በኋላ ኢትዮጵያን ለመው.ረር ተነሳ።
ፋሽ.ስቶች ሕግ ጥሰው ኢትዮጵያን ሲወሩ "ከኢትዮጵያ ጎን እንድንቆም ሐቅ እና ህሊና ያስገደደናል" ያሉ ጥቂት ፈረንጆች ነበሩ። ከነሱ መካከከል አንዱ አዶልፍ ፓርለሳክ ነው።
የቼክ ሪፐብሊኩ ተወላጅ አዶልፍ ፓርለሳክ ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፎ ለመዋጋት ወደ ሐገራችን መጣ። ከፋሽ.ስት ለመፋለም ነፍጥ አነሳ። በረሃ ወርዶ ተፋለመ።
ከአርበኞች ጋር በዱር በገደል ሲንከራተት ከርሞ በጦርነት እሳት ተለብልቦ በመጨረሻም "የሃበሻ ጀብዱ" የተሰኘ መፅሐፍ ያበረከተው ፈረንጁ አርበኛ ሐገራችንን ለመጠበቅ ከአባቶች እኩል ጀብድ ሰርቷል።
ከእለታት በአንዱ አዶልፍ ፓርለሳክ ከራስ ካሳ ጦር ተለይቶ ከጥቂት አጀቢዎች ጋር ሳለ በሽፍቶች ተከበበ። ከኢትዮጵያዊያን አጃቢዎቹ ጋር በመሆን እየተታኮሰ ለመሸሽ ሞከረ። ሽፍቶቹን አምለጠው ተራራ ላይ መሸጉ።
ተራራው ለዘላቂነት የሚኖሩበት አይደለም። ስንቅ የላቸውም። ከታች በሽፍታ ተከባዋል። ከሽፍቶቹ ራቅ ብሎ የወራ.ሪው ጣሊያን ጦር አለ።
የነ አዶልፍ ፓርለሳክ እጣ 3 ብቻ ነው።
አንድ፥ ተራራው ላይ ሆኖ በረሃብ መሞት። ሁለት፥ ተራራው ላይ እንዳሉ በአውሬ ተበልቶ መሞት።
ሦስት በትጥቅም በቁጥርም የሚበልጣቸውን ሽፍታ መፋለም።
የከበቧቸው ሽፍቶች በቁጥር ብቻ ሳይሆን በታጠቁት መሳሪያ ጥራት ይበልጧቸዋል። ከሽፍቶቹ ጥቂት ርቀው የጣሊያን ጦር ሰፈር አለ።
ፓርለሳክ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ጓደኞቹ አንድ ነገር ነግረውታል። "ወደ ኢትዮጵያ አትሂድ፥ እዛ ችግር ቢገጥምህ ሐበሾቹ አሳልፈው ይሰጡሃል" ብለውት ነበር። እሱ ግን አሻፈረኝ ብሎ ከኢትዮጵያውያን ጎን ሆኖ ሊፋለም ወደ ሐገራችን መጣ። አሁን እሱ እና ጥቂት ጓደኞቹ በጠላት ከበባ ወድቀዋል።
ለመፋለም ወሰኑ። ተፋልመን እናምልጥ ወይንም የጀግና አሟሟት እንሙት አሉ። በስፍራው የነበሩቱ "ፈረንጅ ጌታ ፥ አንተ እየመራኸን እንፋለማቸው" አሉት ተስማማ።
ቀጥለው በየተራ መሓላ ፈፀሙለት።
"በሚኒሊክ ስም እምላለሁ፥ እስከመጨረሻው እንፋለማለን። እኔን ሳይገድሉ ለሐገሬ ልትዋጋ የመጣኸውን አንተን አይገሉህም" እያሉ ማሉለት።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ "በሚኒሊክ ስም ቃል እንገባለን። በጀግንነት እንዋጋለን። ሁላችንም ሳንሞት አንተ አትሞትም" አሉት። አመናቸው።
አዶልፍ ፓርለሳክ በመፅሐፉ "በኢትዮጵያ ምድር በሚኒልክ ስም የሚገባ መሓላ ቅዱስ ቃል ነው። ሐበሻ በሚኒሊክ ስም ምሎ የገባውን ቃል በፍፁም አያጥፈውም" በማለት አስፍሯል።
መሓላውን ከፈፀሙ በኋላ በ3 ቡድን ተከፍለው ከከበቧቸው ጋር ተፈለሙ።
ፓርለሳክ ሲጓዝ ከፊት ሁለት ከግራና ቀኝ አንድ አንድ እንዲሁም ከኋላው አንድ ሰው ሆነው ይጓዛሉ። በመሬት ሲሳብ ይሳባሉ። ሲሮጥ ይሮጣሉ። ሲንበረከክ ተመሳሳዩን ያደርጓሉ።
እንዲህ የሚያደርጉት ከየትኛውም አቅጣጫ ጥይት ቢተኮስ ቀድመው ለመሞት ነበር።
በሶት ቡድን የተከፈሉ 20 የሚሆኑቱ ጀግኖች ከበባውን ሰብረው ሲያመልጡ ሁለት ሰው መስዋትነት ከፈለ። ሁለት አርበኞች የጀግና አሟሟት ሞቱ።
"በሚኒሊክ ስም እስከመጨረሻው ጠብታ እዋጋለሁ" ብለው የገቡትን መሓላ ፈፀመው ከከበባ አመለጡ።
ፓርለሳክ ምንድነው ያለው?
"ኢትዮጵያዊ በሚኒሊክ አምላክ ስም የገባው ቃል ቅዱስ ነው። ምንግዜም አይሽረውም"
@Tfanos
በፋሽስ.ት ወረ.ራ ዘመን ቁጥራቸው 15 ሺ የሚሆኑ ተዋጊዎች ከከምባታ በእግራቸው 9 መቶ ኪሎ ሜትር ተጉዘው ወደ ጦር ግምባር ደረሱ።
ከወንድሞቻቸው ጎን ተሰልፈው ለእናት ሐገር አጥንት ለመከስከስ ፥ ደም ለማፍሰስ ፥ የጀግና ሞት ለመሞት የተጓዙቱ የከምባታ አርበኞች መሪያቸው ደጅ አዝማች መሸሻ ይሰኛል።
የሐበሻ ጀብዱ መፅሐፍ ፀሐፊ አዶልፍ ፓርለሳክ እኒህን ልባሞች "ደከኝ የማያውቁ፥ ተወዳዳሪ የሌላቸው ፥ በጀግንነታቸው ወደር የማይገኝላቸው" በማለት ገልጿቸዋል
@Tfanos
ሚኒሊክ ፥ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች
* * *
ይህ ስም ጠቢብ ዲፕሎማት ፥ ሐገር ወዳድ ፥ ባለ ንቁ አእምሮ ፥ ልበ ሩህሩህ፥ ተራማጅ ፥ ወዘተ የሚለውን ተሸክሟል። ሚኒሊክ።
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ የቱጋ ይጀምራል?
አንዳንዶች ከአጤ ቴዎድሮስ ዘመን ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ከሚኒሊክ ይላሉ።
ሚኒሊክን የሚወዱት የሚያውቁት የሚጠሉት ደግሞ የማይክዱት እውነት አለ። እርሱ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ፈጥሯል።
እርግጥ "ዘመናዊት ኢትዮጵያ በቴዎድሮስ ዘመን ተጀመረ፥ መይሳው ካሳ የመሳፍንትን ዘመንን ሲቋጩ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጉዞ ተጀመረ" የሚሉ አሉ።
ሀብታሙ አለባቸው ግን የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች ሚኒሊክ ናቸው ይለናል።
ሀብታሙ "ታላቁ ተቃርኖ" የሚል መፅሐፍ አለው። ይህ መፅሐፍ ያለ ጥርጥር ተስተካካይ የሌለው የትንታኔ መፅሐፍ ነው። ተስተካካይ አልባ መፅሐፍ።
ሀብታሙ "ሚኒሊክ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ፈጠረ" ሲል አራት አስረጂዎችን ያቀርባል።
ዘመናዊት ኢትዮጵያ ስንል...
ሀብታሙ አለባቸው በመፅሐፉ 'ዘመናዊ ሐገረ መንግስት አጀማመር 4 ነገሮችን የሚያካትት መሆኑን በሰፊው ያብራራ ሲሆን እኚህም ፥ የሚታወቅ ብሔራዊ ግዛትና ወሰን፥ በሐገረ መንግስቱ የተጠቃለለ ሕዝብ ፥ መንግስታዊ መዋቅር እና ሉአላዊነት ናቸው
ሀ፥ ብሔራዊ ግዛትና ወሰን
በዘመነ ምኒሊክ የኢትዮጵያ ግዛትና ወሰን ከሞላ ጎደል አለምአቀፋዊ እውቅና አግኝቷል።
ከ1900-1908 ባሉት አመታት 8 ያህል የግዛት /ወሰን/ አለም አቀፍ ውሎችን ተዋውለዋል። ውሎቹ በወቅቱ የኢትዮጵያን አጎራባቾች ቅኝ ከገዙቱ ከእንግሊዝ ፥ ከጣሊያን ከፈረንሳይ መንግስታት ጋር የተደረጉ ነበር።
ለ፥ ሕዝብ
"ሕዝብ እንዲሁ ያለምንም ማብራሪያ ሲታይ አካላዊ ቅርፅ ብቻ ያለው ስብስብ ነው። በአንድ ሐገር ግዛት ላይ የሰፈሩ እና በአንድ ፖለቲካዊ አገዛዝ ስር የተጠቃለሉ" (ገፅ 85)
ሚኒሊክ የተበታተነችን ኢትዮጵያ በማዋህድ ዛሬም ድረስ የቀጠለውን ህዝብ በአንድ የመንግስት መዋቅር ስር ሰብስበዋል።
ሐ፥ መንግስታዊ መዋቅር
ሚኒልክ 'ዘመናዊት ኢትዮጵያን ፈጥረዋል' ሲባል አከባቢያዊ አስተዳደሮችን ነፃነታቸው ተጠብቆ በተሳካ ሁኔታ በአንድ መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ማካተት መቻላቸው ነው።
መ፥ ሉአላዊነት
ሚኒሊክ በተቻለ መጠን የኢትዮጵያ ሉአላዊነት የሚታወቅ እና የሚከበር አድርገዋል።
@Tfanos
".....ለጊዜው እንጂ ለዘለቄታ ደስታ የማይሰጥ፤ ለአጭር ጊዜ እንጂ በቆይታ ህይወትን የሚጎዳ ነገር ሁሉ 'ሱስ' ተብሎ ሊጠቃለል ይችላ። ፍርሃት ፣ ጥርጣሬ እና አምባገነንነትም ከዚሁ ተክለ ቁመና ግራና ቀኝ ኪስ ቢፈተሹ ተደብቀው ይገኛሉ።"
ለሊሳ ግርማ ፥ "ይመስላል ዘላለም" ገፅ 26
@Tfanos
የመግደ.ያ ዛፍ
* * *
በአንድ ዘመን በሐገራችን ኢትዮጵያ ሰዎች እየተሰቀሉ የሚገደሉባት ስመ-ጥር ዛፍ ነበረች፥ የሞት ዛፍ።
ከጥንት ጀምሮ መንግስታት ከባድ ወንጀል ፈፅመዋል ያልዋቸውን በሞት ሲቀጡ ነበር።
ከሞት ፍርደኞች መካከል አንዳንዶች አንገታቸው ላይ ገመድ ሲገባ ሌሎች ደግሞ በሰይፍ ይቀላሉ። ከፍሎቹ ደግሞ የጥይት ሲሳይ ይሆናሉ።
የነገራችን አስረጅ ይሆን ዘንድ የአልሃንድሮ ዴልባዩን "ቀይ አንበሳ" መፅሐፍ ምስክር ጠርተን ወጋችንን እንቀጥል።
አዲሳባ ከጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ከቢጤዎቿ ሁሉ የምትለይ ዛፍ ነበረች። ከሌሎች ዛፎች የለያት ሰዎች የሚሰቀሉባት መሆኗ ነው። የዛፏ ግንዱ ዙሪያውን በሞላ የሰው ገላ ተሸክሟል።
ዴል ባዩ በመፅሐፉ "ይቺ ዛፍ አመቱን ሙሉ የሬሳ ማከማቻ ሆና ታገለግላለች" ብሏል።
የተሰቀሉ ሰዎች በድን ዝናብ ሲወግረው፥ ፀሐይ ሲመታው፥ ነፋስ ሲያወዛውዘው ይውላል።
እጃቸው የፊጢኝ የታሰሩ ፥ አፋቸው ጨርቅ የተወተፈበት ፥ አይናቸው የወጣ አስክሬ.ኖች ይታያሉ። ሬሳቸው የተንጠለጠለበት ገመድ እስኪበጠስ እንደተሰቀሉ ይቆያሉ።
አከባቢው ሞት የሚያንዣብበት ቢሆንም እንቅስቃሴ ይደረጋል። አንዳንድ ሰው ቆም ብሎ የተሰቀሉትን በአርምሞ ያያል። የሆነኛው አስክሬን ላይ ትኩረት በማድረግ ማዘንና ከንፈር መምጠጥም ይኖራል።
በዛፏ አከባቢ አነስተኛ ፍርዶች ይሰጣሉ። ቀማኛ ፥ ማጅራት መቺ፥ ወዘተ እንደየጥፋቱ ይቀጣል። እንደ ፍርዱ ደረጃ አንድ እጅ ይቆረጣል ወይም አንድ እግር አሊያም ሁለቱም ይቆረጣል። ጆሮ እና ምላስም እንደአላስፈጊ ነገር ተቆርጦ ሊወገድ ይችላል።
ከእለታት በአንዱ የጎሳ አለቃ የነበረ ተዋጊ በርካታ ወታደሮችን ከገደለ በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለ። ለፍርድ ቀርቦ ሞት ተፈረደበት። በዛፏ ላይ ተሰቀለ። በተሰቀለበት አይኖቹን አሞሮች በሉት
@Tfanos
ጥሩ የሰሩ ሰዎችን ማሞገስና ማድነቅ የማይሆንላቸው አሉ። አድናቂዎችን "አሽቃባጭ" ሲሉ ሃፍረት አይሰማቸው።
በተቃራኒው ዝነኛ ሰዎች ምንም ቢያጠፉ መወቀስ የሌለባቸው የሚመስላቸው አሉ። ዝነኞችን መተች "ቅናት" ይመስላቸዋል።
ማድነቅ ማሽቃበጥ እንዳልሆነ ፥ መተቸትም መቅናት እንዳይደለ የሚያስተምር ያስፈልግ ይሆን ?
@Tfanos
ጃንሆይ፥ በሀረማያ ወንዝ ሰጥመው ከመሞት የተረፉት ንጉሥ
* * *
ንጉስ ሃይለስላሴ ሳይባሉ በፊት ተፈረሪ መኮንን ሳሉ ነበር የሀረር ገዥ ሆነው የተሾሙት። ከእለታት በአንዱ የሀረር ገዥ ሳሉ ሞትን ተጋፈጡ፥ ወንዝ ላይ ሰጠሙ። ንጉሰ ነገስት አፄ ሃይለስላሴ በወጣትነታቸው ውሃ ሊወስዳቸው ሆነ
የነገራችን አስረጅ ፥ የወጋችን ማስረጃ ይሆነን ዘንድ በአፄ ሃይለስላሴ የተፃፈውን "ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ" ቅፅ አንድ መፅሐፍን ምስክር ጠርተን እንቀጥል
በሀረር ሳሉ መርዶ ተነገራቸው። የባለቤታቸው መነን ወንድም የሆኑት ራስ ሀይሉ ማረፋቸው ተሰማ። መነን የወንድማቸውን ለቅሶ ለመድረስ ወደአዲስ አበባ ጉዞ ጀመሩ። ራስ ተፈሪ መኮንን (አፄ ሀይለስላሴ) እስከሀረማያ ድረስ መነንን ሸኙ።
ተፈሪ መኮንን ወደ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት በሃረማያ ሃይቅ መዝናናትን ፈለጉ። መኳንንት እና መሳፍንትን አስከትለው ወደ ውሃው አቀኑ።
በሀረርና በድሬዳዋ የሚኖሩ ሰዎች በተለይ የውጭ ዜጎች የሚንሸራሸሩባት ጀልባ ላይ ለተዝናኖት ተመረጠች። ከተፈሪ ጋር 10 ሰዎች በጋራ ጀልባዋ ላይ ተሳፈሩ።
ድንገት ግን አደጋ ተፈጠረ። በውሃው መሃል ሳሉ ጀልባዋ ተቀደደች። ውሃ ገባ። አደጋ መጣ። ሞትን የሚወልድ አደጋ!
በጀልባው ያሉ ሰዎች በድጋጤ ብዛት ህይወታቸውን ለማዳን መሞከራቸውን ቀጠሉ። ጀልባዋ ላይ የሚገባውን ውሃ በባርኔጣቸው እየቀዱ መድፋት ጀመሩ። ግን መፍትሄው አልሰራም። ጀልባዋ መስጠም ጀመረች
ተፈሪ መኮንን እና አብረዋቸው የነበሩቱ ሁሉ ወደ ውሃው ዘለሉ። ቀጥሎ የጭንቅ ዋና ተጀመረ። ዋናው ፈታኝ ነበር። ሰባት ሰዎች ደክመው ሰጠሙ።
ሰዎች መስጠም ከጀመሩ በኋላ ከውሃው ዳር ያሉ መኳንንት እና ሰራዊት የተፈጠረውን አስተዋሉ። ጊዜ አልፈጁም። እየዘለሉ ገቡ፥ ወደ ሃረማያ ሀይቅ።
ተፈሪ መኮንን (ሃይለስላሴ) በሰዎች እርዳታ ከሞት ቢተርፉም ሰዎችን መለየት የማይችሉበት ደረጃ ደርሰው ነበር። ሙሉ ለሙሉ የነቁት አደጋው በተፈጠረ ማግስት ነበር።
@Tfanos
ስለ ጴንጤ ዘማሪዎች......
* * *
ፓስተር ታምራት ሀይሌ ሻሸመኔ ለአገልግሎት ተጋብዞ መጣ። ከርሱ መማር ፥ በጊታር ሲዘምር መስማት የማያጓጓው ማን አለ? ለታሜ ብዬ ቸርች ለመሄድ ወሰንኩ። መዋሸት የማያስፈልገው እውነት ቸርች መሄድ አቁሜያለሁ። ቸርች አለመሄድ ጀብድ ሆኖ ሳይሆን እውነታው ለአመታት አለመሄዴ ነው። ከአመታት በኋላ ቸርች ሄድኩ።
አምልኮ ሊጀምር ሲል ደረስኩና ወጣሁ።
የመዝሙር ሰኣቱ ሲያልቅ ለመመለስ ወጣሁ።
ወጣት ዘማሪዎች ያናዱኛል። ባለውቃቢ ይመስል መድረክ ላይ ያጓራሉ፥ ቸርቹን ጭፈራ ቤት ሲያደርጉት ሃፍረት አይሰማቸውም ፥ በጉባኤ መሐል መደነስ ብልግና መሆኑን አያውቁም፥ ሰይጣን እንደያዘው ሰው መጮህ መንፈሳዊነት ይመስላቸዋል።
ቸርች መሄድ ከማቆሜ በፊት ብዙ ዘማሪዎችን "ለምንድነው ስነስርኣት የማይኖራችሁ?" እላቸው ነበር። ቸርች መሄድ ከማቆሜ በፊት መንፈሳዊ ግጥም ለማቅረብ ሄጄ ፉጨቱ እና ወከባው አናዶኝ ''ስርኣት አልበኛ አትሁኑ" ብዬ መድረክ ላይ ተናግሬ አውቃለሁ። ቸርች መሄድ ከማቆሜ በፊት ለተለያዩ ፓስተሮች ''የዘማሪዎችን ስርኣት አልበኝነት አስታግሱ እንጂ'' ብዬ አውቃለሁ። ኋላ ላይ ሰልችቶኝ ተውኩት።
አንዳንድ ሰዎች እንደፈለጉ የመዘመር መብት ያላቸው ይመስላቸዋል። እንደፈለጉ የመሆን መብት የለም። እንደወደደው መሆን የሚሻ ሰው ዘማሪ ሳይሆን ዘፋኝ ይሁን። ዘማሪ ግን ለሰው አእምሮ የመጠንቀቅ መንፈሳዊ ሃላፊነት አለበት።
ክርስትና ምንድነው ? ክርስቲያን በክርስቶስ ያገኘው ነፃነት ምንድነው ? ፀጋ ምንድነው ? ወጣት የጴንጤ ዘማሪዎች ይሄን መማር አለባቸው።
የቀደሙቱ ጥራት ባለው ህይወታቸው ጭምር ያገለግሉ ነበር። የአሁኖቹ ደግሞ በህይወታቸው ብዙዎቹን ያሰናክላሉ።
ስለ ዘማሪዎች አነሳን እንጂ ጴንጤው ማህበረሰብ ስለገጠመው ውድቀት ብዙ ማለት ይቻላል።
የትላንቱ ጨዋነት የት ገባ? የቀደመውን ትህትና የቀማ ማን ነው? ያለፈውን ስነስርአት ምን ወሰደው ?
@Tfanos
ሰሞኑን በወለጋ ሆሮ ጉድሩ ሙሉወንጌል ቤተክርስቲያን ላይ የድሮን ጥቃት ተደርጎ ነበር። በጥቃቱ 8 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
መቼስ መንግስት 'ንፁሃንን አይጉዳ፥ የሃይማኖት ተቋማትን ያክብር' ብሎ መጠየቅ ቅንጦት ሆኖብናል።
@Tfanos
"ማነህ ደመቀ"
"አቤት ጌታዬ"
"ገንዘብ ሚኒስተሩን 'ዶክተር አብይ አንድ ቢሊዮን ብር ላክ ብሎሃል' በለው"
"ጌታዬ ያን ያህል ብር የለንም"
"አዲስ በገዛነው የብር ማተሚያ ማሽን አትሙ በቃ"
@Tfanos
@Tfanos