#በትናንትህ_ማንም_እንዲያሸማቅቅህ_አትፍቀድ!!
ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ትናንት አለው። ትናንቱ ደግሞ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን ይቻላል። ሁሌም ሰዎች ነገህን አይተው አይሰድቡህም ነገህን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነውና ከዚያ ይልቅ የሚያደርጉት ባለፈው ማንነትህ ላይ ከነበረህ ስህተት ወይም ውድቀት ወይም አለመሳካት ነው። ሐጢያት ሰርተህ ከነበረ በዚያ ንስሐ ገብተህ ከተመለስክ፣ የተለያዪ የማጣት፣ የመውደቅና የመነሳት ታሪክ ከነበረህ እና አሁን ከተነሳህ እንኳን ተነሳህ። ዋናው እሱ ነው።
በትናንት ማንነት የሚያሸማቅቁህ ሰዎች ነገህን የመያዝ አቅማቸው ከፍተኛ ነው ከፈቀድክላቸው። በትናንት በምንም አይነት መንገድ ሒድ ምንም አይነት ሐጢያት ስራ ከተመለስክ ራስህን ካረምክ ጉዞህ ወደፊት መሔድ ብቻ ይሁን። የበፊቱን ስህተት ዛሬም እየደጋገምከው አትኑር። በባለፈው ስህተትህ ታንቀህ አትኑር።
ሰይጣንና ክፉ ሰዎች ሁሌም የሚቆጥሩት ትናንት የወደክበትን ወድቀት ነው። እግዚአብሔር የሚያየው ደግሞ መነሳትህን ነው። ሞክረህ ባልተሳኩልህ ነገሮች፤ ሳታውቅ ባጠፋሃቸው ጥፋቶች፣ መርጠህ ባልመጣህባቸው የህይወት ጎዳናዎች ምክንያት ሊያሸማቅቅህ የሚመጣውን አትቀበል።
ሰዎች ሁሌም የሚያሳዩህ ትናትህን ነው አንተ ነገህንና ተስፋህን አሳያቸው። ሰዎች ትናንት እነሱ ቤት የበላህውን ምግብ ሲቆጥሩ እና ሊያሳጡህ ከሞከሩ፣ አንተ ነገ ብዙዎችን መመገብ የሚችለውን ራዕይህን አሳያቸው። ሰዎች በትናንትህ እንዲያሳንሱህ አትፍቀድ፣ ትናንት እኮ ትናንት ነው። ሰዎች አንተ አሳንሶ ለማሳየት ይሁን ወይም በባለፈው ህይወትህ ለማሳጣት ከፈለጉ አንተ ደግሞ ዛሬህ ላይ በመስራት ነገህን አሳያቸው።
፨ ትናንት በነበረህ የኑሮ ደረጃህ
፨ በዘርህና በሐይማኖትህ
፨ በስህተትህ / ሁሌም ስህተትን ለማረም እና ከስህተት ለመማር ዕድል አለ
፨ በህይወት በሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶችህ
፨ ሞክረህ ባልተሳካልህ ነገሮች
በአጠቃላይ በትናንትናህ ማንም እንዲሸማቅቅህ አትፍቀድ!! መልካም ምሳ!
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs