#እኔ_አውቅልሃለሁ!!
አንዳንድ ሰዎች ሰዎችን ከሚያጠምዱበት መንገድ አንዱ "እኔ ነኝ የማውቅልህ" የሚሉ አመለካከትና ድርጊታቸው ነው። አንተ ስለ ራሰህ አታውቅም እኔ ግን ስለ አንተ አውቃለሁ ይሉሃል። እኔ አውቅሀልሃለሁ ማለት አንተ ስለ ራስህ ምንም አታውቅም ማለት ነው። የእነዚህ አይነት ሰዎች ምልክቶች
፨ አንተ እንዲህ ነህ ይሉሃል፦ እኔ እንዲህ ነኝ ከምትለው ይልቅ እነርሱ እንዲህ ነህ በሚሉት ነገር ደምድመው ጨርሰው ስለ አንተ ለአንተ የሚያስረዱ ናቸው። ለአንተ አንተን ይተርኩልሃል። የእነዚህ አይነት ሰዎች አደጋው አንተን ሳትሆን እነርሱን የፈጠሩትን አንተን ይነግሩሃል። ደምድመው በዚያ ልክ ይሰፉልሃል።
፨ ይቃወሙሃል፦ እነርሱ ነህ ከሚሉህ ውጪ ስትሆንና ራስህን መቀበል ስትጀምር ደግሞ ይቃወሙሃል ከዚያም ያጣጥላሉ። ሰዎች ሁልጊዜ እነርሱ ነህ በሚሉህ ስትመላለስ ደስተኞች ናቸው አይደለሁም ብለህ የራስህን ማንነት ተቀብለህ ስትሄድ ይቃወሙሃል ያኮርፉሃል ያገሉሃል።
፨ ስኬትህን አይቀበሉም፦ እነዚህ አይነት ሰዎች እነርሱ ከሚሉህ ውጪ ስትሆንና ከሰፉልህ ልክ ስትወጣና በራስህ መንገድ ስኬታማ ስትሆን ያንን ስኬት መቀበል አይፈልጉም። የአንተ እውነተኛ ማንነት መቀበል ስለማይፈልጉ ስኬታማነትህን ይገፋሉ። የምትናገረውን መቀበል አይፈልጉም በእነርሱ ሐሳብ ቁጥጥር ውስጥ እንድትሆኑ ብቻ የእናንተን ማንኛውም ነገር በማጣጣል ይሄዳሉ።
ስለ ሰዎች በተወሰነ መልኩ ልናውቅ እንችላለን ሰዎችን ግን አውቀን ልንጨርስ አንችልም። አውቅልሃለሁ የሚሉህ ሰዎች እነርሱ በቀደዱልህ ቦይ ብቻ እንድትፈስ ይፈልጋሉ ከዚያ ወጥተህ ራስህን በቀደድከው መንገድ ስትሄድ ደግሞ በፍጹም አይቀበሉህም። ሁልጊዜም ከሰዎች የምንማረው ነገር ቢኖርም ሰዎች በፈጠሩልን መንገድ ግን እንድሄድ አልተፈጠርንም። የበላይ የመሆን፣ ሰዎችን በቁጥጥር ስር የማድረግ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የሚንጸባርቁት አንደኛው ነገር አውቅልሃለሁ ማለትን ነው።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#የበታችነት_መንፈስ- #አደገኛው_በሽታ!!
©ዘሪሁን ግርማ
ከጥቂት አመት ወዲህ እየገባኝ ከመጡ ነገሮች መሐል የበታችነት ስሜት ያለባቸው ሰዎች ያሏቸውን አደገኛ ባህሪያት አስተውያለሁ። ሁላችንም በተለያየ ምክንያት የዚህ ስሜት ተጠቂ ሆነን ልናድግ እንችላለን። በቤተሰብ መሐል ባለ አስተዳደግ፣ በሰዎች በደረሰብን ጫና፣ በመናፍስት ጥቃት እና በተለያዩ ምክንያቶች የዚህ መንፈስ ተጠቂ ልንሆን እንችላለን።
ማንኛውም ሰው፤ እንዲሁም የቤተክርስቲያን መሪ ሆነው ወይም አገልጋይ ሆነው በዚህ መንፈስ ከተያዙ ደግሞ ወዲያው ነቅተው ይህን ችግር ካልቆረጡት ለብዙ ችግር ይዳርጋቸዋል። በእኔ ምልከታ በበታችነት ስሜት የተያዙ ሰዎች በእኔ'ነት (ስለራሳችው የተጋነነ አመለካከት) ካላቸው ወይም በትዕቢት ከተያዙ ሰዎች ይለያሉ። እኔ'ነት ወይም ትዕቢት ለውድቀት የሚዳርግ ትልቅ ችግር ሲሆን የበታችነት መንፈስ መጠቃትም ሌላው ችግር ነው። የበታችነት መንፈስ ያለበት ሰው ያሉበትን አስቸጋሪ ባህሪያት በሙሉ ባላውቅም እኔ የገቡኝን በጥቂቱ ላስቀምጥ።
፨አጉል ድፍረት፦ የበታችነት መንፈስ ከባድ ችግር በውስጣችን በሚፈጠር ያለመፈለግ፤ እናቃለሁ ብሎ የመፍራት፤ እበለጣለሁ ብሎ፣ አይወዱኝም ብሎ በማሰብና በሌሎች ምክንያት ውስጥ ከሆንን ያንን በውስጣችን ያለውን ትግል ለማሸነፍ አጉል ደፋር መስሎ ለመታየት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማሳየት እና ማድረግ ያጠቃልላል። ጤናማ ድፍረት ችግር ባይኖረውም በውስጣችን ያለውን የበታችነት ስሜት ለመሸፈን የምናንጸባርቀው አጉል ድፍረት ብዙ ነገራችን ይባስ ያበላሻል።
፨ አግላይ መሆን፦ ብዙ የበታችነት ስሜት የሚመጣው ከኃላ ካለፍንባቸው መንገዶቻችን ተሞክሮ ስለሆነ የበታችኝነት ስሜት ሰዎችን የማግለል ችግርን ይዞ ሊመጣ ይችላል። አብሶ በቤተክርስቲያን ስራ ውስጥ እግዚአብሔር አብረውን እንዲሰሩ በተለያዩ ምክንያት የሚሰጠንን ሰዎች በእበለጣለሁ ወይም እቀማለሁ በሚል እሳቤ ሰዎቹን የመግፋት እና የማግለል አኪያሄድ ሊኖረን ይችላል። አቅራቢና አቃፊ መሆን ትልቅ ነው። ብዙዎች በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር የሰጠንን ሰዎች ልናጣ እንችላለን።
፨ አልችልም ማለት፨ በዚህ ስሜት የሚጠቁ ሰዎች ሌሎችን ትልቅ ራሳቸውን ትንሽ፣ ሌሎች የሚችሉ እነርሱ የማይችሉ እንደሆኑ ያስባሉ። በሁሉም ነገር በሰዎች ላይ ተንጥልጥለው መራመድ እንጂ ራስን በራስ ለማቆም እችላለሁ ብለው አያምኑም። አልችልም ብሎ ማሰብ አደጋ ነው። በእርግጥ የማንችላቸው ነገሮች የሉም ለማለት ሳይሆን አልችልም በሚል መንፈስ መያዝ ግን አንደኛው የበታቸኝነት ስሜት መገለጫ ሊሆን ይችላል።
፨አዋቂ መምሰል፨ አለማወቅ ችግር አይደለም ለማወቅ አለመፈለግ ነው ችግር። ሁልጊዜም ሰዎች የማናውቃቸው ነገሮች ይኖሩናል። በዚህ መንፈስ የተጠቁ ሰዎች ሳያውቁ እንደሚያውቁ እና ማንም ሳዬጠይቃቸው አዋቂ እንደሆኑ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ።
፨ ያልተገቡ ድርጊቶች (Over Acting)፨ ብዙ በጉራ እና በውጫዊ ነገር ብቺ ራስን ለማሳየት የሚደረግ ድርጊት፣ ቀደም ቀደም ማለት፣ ባልተገባ ቦታ እንደሚችሉ ለማሳየት መሮጥ፤ በሆነ ነገር ይበልጠናል ብለን በምናስባቸው ሰዎች ፊት "እርሱ እንዲህ ነው" እንዲሉን የምናሳየው ያልተገባ ድርጊት እንደኛው ምክንያት የበታችነት ስሜት ነው።
ሰው ከዚህ መንፈስ በእግዚአብሔር ቃል በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ሊፈወስ እንደሚችል አምናለሁ። በአጭሩ የበታችነት መንፈስ " ራስን በትክክለኛ መንገድ እና እውቀት አለመቀበል ነው" ለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል እና መጸለይ ፍቱን መድሃኒት ናቸው። ስለ ራስ ያልተጋነነ ግን ትክክለኛ አመለካካከትን እንደ እግዚአብሔር ቃል ራሳችንን ላይ እንገንባ።
“ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤”
— ኢሳይያስ 40፥4
/channel/theideaofs
በሰው ውድቀት አትደሰት፣ በሰው ስኬት አትቅና፣ ለሚያልፍ ነገር ወዳጆችህን አትተው፣ ለወዳጆችህ የሚልፈው ነገር አሳልፈው፣ ታገስ፤ ትንሽ ትዕግሥት ብዙ ማትረፊያ ናት።
መልካም ዕለተ ሰንበት!
/channel/theideaofs
#ፍጻሜ_ከሌለው_በሰዎች_ከመታመን_ህይወት_እንውጣ !
በሰው ላይ የተመሰረተ ህይወት፣ ክርስትና፣ በሰው ላይ የተመሰረተ ደስታ ፍጻሜ የሌለው እና የማይጸናም ነው። በሰዎች ላይ የምንመሰርተው ማንኛውም ነገር መጨረሻው ሐዘን ነው። ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት ወደ ህይወታችን ይመጣሉ ጥሩ አብሮነት ከእኛ ጋር ሊመሰርቱ ይችላል። ሰው በራሱ የራሱ የሆነ ትግል ይኖረዋል ለመደገፍ የሚበቃም አይደለም። አንድ ቀን ሊሰበር፣ ከእኛ ሊለይ እና ሊርቀን ይችላል።
ሰዎች በእኛ ህይወት እጅግ አስፈላጊ ክፍል (Role) ቢኖራቸውም እንኳ ደስታችንና ነገአችንን በእነርሱ ላይ መመስረት አንችልም። ምክንያቱም ሰው ውስን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት የተለያዩ ቃሎችን በእንዲህ ያካፍለናል፦
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው።”
— ኤርምያስ 17፥5
በሰው ታምኖ በእግዚአብሔር ከመታመን የተመለሰ ሐይሉን በስጋ ለባሽ ላይ የሚመሰረት ሰው ከርግማን በታች ነው። ይለናል። ሰው ምንም ጥሩ ቢሆን፤ ምንም ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ መልካም ሰው ቢሆን ልንታመንበት የማይበቃ ነው። መጽሐፍ ቅዱሱ አያይዞ ም እንዲህ ይለናል፦
ኤርምያስ 17
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
⁸ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።
በሰዎች ላይ ታምነን እና ተደግፈን የነበርን በሰዎቹ አለመታመን የተጎዳን ሰዎች ካለን፤ ምክንያቱ ሁለት ነው። የመጀመሪያው፦ ሰው እንድንደገፈው የማይገባ ሰውን ለማደገፍ የማይበቃ ለራሱም ድጋፍ ፈላጊ ስለሆነ ሲሆን ሁለተኛው፦ እግዚአብሔር እምነታችንን እና መደገፋችንን በሰዎች ላይ እንድመሰርት ስለማይፈልግ ነው።
የታመንበት ሰው ከሆነና በዚያም እየቆሰልን ያለን ካለኖ አይናችንን ከሰዎች ላይ ማንሳት አለብን። አይናችንን በማይጥለው፣ በማይሰለቸው፥ እኛን ለመሸከም ፍቅርና ትዕግስቱ ባለው፣ ምላሽ ሊሰጠን በሚችለው በእግዚአብሔር ላይ እንታመን አይናችንን በእርሱ ላይ እናድርግ።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#በህይወትህ_ማወቅና_መከተል_ያለብህ_ሶስት_ነገሮች
፨ በማያገባህ ጉዳይ አትግባ
፨ በራስህ ነገር ላይ አተኩር
፨ ሁልጊዜም ለሰዎች መልካምን አድርግ
#በማያገባህ_አትግባ፦ በሰዎች ጉዳይ ሆነ በማንኛውም ነገሮች ውስጥ በማያገባህ ጉዳይ ውስጥ አትግባ። ብዙ ጊዜ ዋጋ የምንከፍለው በማያገባንና በማይመለከተን ነገር ላይ ስለምናተኩር ነው። እኔ በማያገባኝ ገብቼ ዋጋ ከፍዬ አውቃለሁ። ብልህ ሰው ማለት በማንኛውም ሁኔታው የሚመለከተውን እና የሚያገባውን ብቻ የሚያደርግ ነው።
#በራስህ_ነገር_ላይ_አተኩር፦ በራስህ ስራ፣ አገልግሎት፣ ራዕይና ግንኙነት ላይ አተኩር። የራሱን ነገር ላይ ማተኮር እንደ ጥቅስ ቀላል የምትመልስል አባባል ብትሆንም በድርጊት ግን ብዙ ራስን ማዘጋጀት ይጠይቃል። በራሳቸው ነገሮች ላይ ማተኮር የሚያቅታቸው ሰዎች በሌሎች ጉዳይ ውስጥ ይጣዳሉ ወይም አትኩሮታቸው በማይመለከተው ነገር ይያዛል።
#ሁልጊዜም_ለሰዎች_መልካምን_አድርግ፦ መልካም ማድረግ ሰዎችም መጥቀም ብቻ ሳይሆን የእኛን ስነ ልቦና ጭምር ትክክል ያደርገዋል መልካም ነገር ከመልካም ልብ ይፈልቃልና። ምንም ነገር ቢያጋጥምህ ከመልካምነት እንዳትጎድል መልካምነት መልካም ዘር ነውና። በሚመችም በማይመችም ሁኔታ ውስጥ መልካምን ነገር ሌሎች አድርግ።
እነዚህ የህይወት መርሆች እኔን ጠቅመውኛል እናንተንም ይጠቀማል ብዬ አስባለሁ። ብሩካን ናችሁ።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#የታገሉን_ነገሮች_የተመሰገኑ_ይሁኑ!!
በስፓርት አለም ጡንቻ የሚወጣው የሰውነት አካላችንን በማትጋት በማሰራት ነው። የእጅ፣ የእግር፣ የትከሻ ሌሎችም ጥንካሬና ቅርጾች ያለ ፍጋት አይመጡም። አካላችን ቅርጽ የሚይዘው ስናታግለው ነው። የእኛም ማንነት የሚሰራው በሚያታግሉት ነገሮች አንጻር ነው። ሰውን አጉል ወደድንህ ከሚሉት፣ ከሚያንቆለጳጵሱት ይልቅ የሚተቹት፣ የሚገስጹት ፣ የማይቀበሉት ይሰሩታል። ጠንቃቃ አስተዋይና ብርቱ ያደርጉታል።
በህይወታችን የሚመጡ ነገሮችን ለመልካም ከተጠቀምንባቸው ማንነታችንን የሚሰሩ ይሆናሉ። በተለያየ መንገድ ወደ ህይወታችን የሚመጡ አብረን በስራ፣ በአገልግሎት በማንኛውም መንገድ ያገኘናቸው የሚታገሉን ከሆነ እየሰሩን ነው። እዚህ ጋር የሚታገሉንን በሁለት መንገድ ማየቱ ጥሩ ነው።
#የመጀመሪያዎቹ፦ ለእኛ አስበው እኛ በማንፈልገውም መንገድ ቢሆን የታገሉን፤ ያረሙን የገሰጹን፤ የተቹን ስህተታችንን ያሳዩን በሚያስፈልገው የሚያግዙን ወዳጆቻችን ይቀርጹናል። እንደነዚህ አይነት ሰዎች በእነዚያ ጊዜያት ባይመቹንም፤ የህይወታችን ጀግኖች ይሆናሉ። እኔ እንደዚህ አይነት ወዳጆች አሉኝ። እነርሱን እጅግ አመሰግናለሁ።
#ሁለተኛዎቹ ደግሞ የሚጠሉን፤ የማይረዱን፤ ሊቀበሉን የማይፈልጉ፤ ስህተታችንን እያነሱ የሚተቹን ሰዎች እነዚህኞቹም ካወቅንበት ራሳችንን ለመስራት ድልድይ ናቸው። እንደ እነዚህ አይነት ሰዎች በስህተት እንዳንገኝ ጥንቃቄን፤ ተሳስተን ከነበረም መታረምን፤ ሲጎዱን ይቅርታን፤ ሲገፉን ጥንካሬን፤ ሲጥሉን መነሳትን፣ ሲከዱን ጥበብን፤ ብቻችንን ሲተዉን ለብቻ መጓዝን፤ ስም ሲያጠፉ መጽናትን፣ እንደነዚህ አይነት ሰዎች በእግዚአብሔር እንድንታመን፤ በራሳችን እንዳንመካ፣ ልቅ እንዳንሆን ያደርጉናል። ማንነታችን ቅርጽና ጥንካሬ የሚያዳብረው የሚታገን ካሉ ብቻ ነው።
"ሰውን ከስኬቱ ይልቅ ውድቀቱ ትህትናን ያስተምረዋል። ከአጉል ወዳሴ ይልቅ ትግሎች ያጠነክሩታል።"
®ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#በይቅርታ_የሚገኝ_ፈውስ!
ይቅር እንበል ወይስ እንሽሽ?
" እያንዳንዱ ሰው ይቅር የሚለው ሰው እስኪያጋጥመው ድረስ፣ ይቅርታ ተወዳጅ ሐሳብ መሆኑን ይናገራል።"
ሲ.ኤስ.ሌዊስ
ባለፈው ስለ ይቅርታ በጻፍኩት ፅሑፍ ላይ ይቅርታ በማድረግ ስለምናገኘው የህይወት ፈውስ ትንሽ ሐሳብ አስቀምጬ ነበር ዛሬ ደግሞ ይቅር እንዴት እንበል? ማንን ይቅር እንበል? ግዴታ ነው ወይ ? እንችላለንንስ የሚለውን በጥቂቱ እናያለን፡፡
ብዙ አንድ ጊዜ የጎዳንንና በጣም ሳይቀርበን በተለያየ ነገር የጎዳን ላይ ብዙ ቂም ወይም ጥላቻ አንይዝም (በጉዳቱ አይነት ቢወሰንም) ወይም ቶሎ እንረሳዋለን፡፡
የምናምናቸው ሰዎች ፤ የምንቀርባቸው ሰዎች ፥ ቤተሰቦቻችን፥ እጮኛዎቻችን፥ ወይም የስራ አጋራችን ሲጎዳን ይቅር ማለት አንችልም ወይም ምርጫችን ማድረግ አንፈልግም፡፡ ምክንያቱም የጉዳት ልክ የሚወሰነው በገነባነው ቅርበት ላይ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በቅርብ ሰው፣ በምናምነው ሰው የሚፈጠር ጉዳት ከባድ ነው።
የይቅርታ ጉዞ ሰውን በክርስትናው የበሰለ እንደሚያደርገው እርግጥ ነው፡፡ ይቅርታ ማድረግ ያደገ ክርስቲያን መገለጫው ነው፡፡ ያንተ ይቅርታ የሚያስፈልጋው ሰዎች ካላንተ ይቅርታ ማድረግ ፈውስ አያገኙም። አንተም ለእነርሱ ይቅርታ ካላደረክ ተበድለክም ታስረክም ትመላለሳለህ፡፡ ይቅርታ በህይወትህ ልትመርጠው የሚገባህ ምርጫህ ነው፡፡ አንተ የማትበድል ሰው አይደለም፥ ሰውም እንደ አንተ ነው ፡፡ ይበድላል፤ ይዋሻል፡፡
ኢየሱስ ስለ ይቅርታ ከተናገራቸው ነገሮች አንደኛው ክፍል ይገርመኛል፡፡ በማቴ 6 ላይ የአባታችን ሆይ ፀሎትን ሲያስተምራቸው፦
" እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን " ብሎ አስተምራል፡፡
ኢየሱስ ያለውን አስተውላችሁታል? እኛም ይቅር እንደምንል ..ይቅር በለን ነው ያለው እንጂ ይቅር በለኝና ይቅር እላለው አላለም፡፡ ስለዚህ ይቅርታ ማድረግ የእኛን ይቅርታ (ከጌታ ዘንድ) የመቀበያ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ ይቅር ካላልክ ይቅር አትባልም፡፡ ማር 11;25-26 ይመልከቱ፡፡
ሌላው በይቅርታ ማድረግ ውስጥ ከባዱ ነገር የተበደልነው ነገር ክብደት ነው፡፡ በስራ ባልደረባው በውሸት ተከሶ እስር ቤት የማቀቀ፥ በትዳር አጋሩ ተከድቶ ህይወቱ የተበላሸ፥ በመጋቢዎቹ ተገፍቶ ነገሩ የተጎዳ፥ አገባታለው ብሎ ዎጋ የከፈለላት እጮኛው የካደችው፤ ቤተሰቦቹ ገፍተውት ለብቻው የኖረ፣ ያመናቸው ሰዎች ስሙን የጠፉበት ሰው ይቅርታ ማድረግ አለበትን? ይቅርታ ማድረግ ይችላልን? መልሱ አዎን ነው የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረን ያንን ነውና። ከባድ አይደለም ማለት አይደለም ከፈቀድን በእግዚአብሔር ጸጋ የማይቻልም አይደለም።
እግዚአብሔር እኮ ይቅር እንዳንለው የዘጋው በደል የለም፡፡ በእኛ በቀል የእኛ ነገር እንደሚፈወስ የምንፈልግ ሰዎች ከበፊቱ የባሰ ስህተት አኪያሄድ ላይ ነን፡፡ ይቅርታ ያለማድረግ የተበደልነው አይፈወስም፡፡ አንዳንዶቻችን ስንበደል እንሸሻለን እንጂ ይቅርታ አናደርግ፡፡ መቶ ሺህ ሜትሮች ርቀን እንኳን ሰውየውና በደሉን አቅፈነዋል ስለዚህም ህመሙ በውስጣችን እያደገ መልኩን ወደ ጥላቻ ከዚያም ወደ በቀል ሊያድግ ይችላል።
አንድ ሰው ከምንም በላይ ይቅርታ የማድረግ ውሳኔና ልብ ካለው እግዚአብሔር ይረዳዋል፡፡ አንዳንድ ቁስሎች ለመሻር ጊዜና
ይፈልጋሉ ከወሰንን ግን እግዚአብሔር ይረዳናል፡፡ አንዳንድ ነገሮችንም ይቅር ለማለት አቅም ልናጣ እንችላለን የእግዚአብሔር ጸጋ ግን ላረዳን ይችላል።
ብዙ ሰዎች ሲበደሉ ፤ እነርሱ ደግሞ የበደላቸውን ይቅር ባለ ማለት ይበድላሉ፡፡ ራሳቸውን ሲጎዱ፥ ባልጀራቸውን ያስራሉ ፥ ጌታን ይበድላሉ፡፡ "ሳል ይዞ ስርቆት፥ ቂም ይዞ ፀሎት (አይቻልም) " አይደል የሚባለው፡፡ ከጥላቻ እና ከቂም ጋር ያለ ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሌለው ነው።
መግቢያዬ ላይ ያነሳሁት የሲ ኤስ ሌዊስ አባባል በአፋቸው "ይቅር ብያለው"ለሚሉ ሰዎች ሳይሆን በእውነት ይቅርታ ለማድረግ ለሚታገሉ ሰዎች የተነገረ ነው፡፡ ይቅርታ ማድረግ በአፍ ቀላል ነው፡፡ ድርጊቱ ግን ውሳኔና መሰጠት ይፈልጋል፡፡
እኛ ክርስቲያኖች ነን፡፡ ይቅርታ ማድረግ ግዴታችን ነው፡፡ ጌታስ ስንቱ ነገራችንን ይቅር ብሎን የለ፡፡ እሱ አስቀድሞ በይቅርታው ባያገኘን ኖሮ ፤ ዛሬ ይቅርታ እናድርግ አናድርግ የሚል ሰጣ ገባ ውስጥ አንገኝም፡፡ እኛ ቀድሞ በሐጢያተኛ ተፈጥሮ ማንነታችን ሞተን ነበርና፡፡ ሌላው ማወቅ ያለብን ሰዎች ሁሌም የሚጎዱን አስበውት አይደለም እንዳንዶቹ ባለማወቅ፣ አንዳንዶቹ አቅም በማጣት አንዳንዶቹ ባለመለወጣቸው እና በተለያየ ምክንያት ነው።
እኛም በቀጥታም በተዘዋዋሪ ሌሎች ሰዎችን እንበድላለን፣ ወይም እናስቀይማለን። የእኛ ይቅርታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ የእነርሱ ይቅርታ የሚያስፈልገን ሰዎችም አሉ።
.......ይቀጥላል......
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#የመሪ_የውስጥ_ተግዳሮቶች!!
ሁሉም ሰው መሪ መሆን አይችልም፣ ለመሪነትም ሁሉም አይጠራም። መንፈሳዊ አገልጋይ መሆንና መሪ መሆን ይለያያል። ሰው መስበክ ስለቻለ ወይም መዘመር ስለቻለ መሪ ነው ማለት አይደለም። ለዚህም ነው የመሪነት ስብዕና ከሌሎች የተለየ ነው። መሪዎች በባህሪያቸው የተለያየ እይታ አለካከትና ለሰው ጭምር የማይገቡ አኪያያሄድ አላቸው።
መሪ ሰዎችን የማስደሰት አላማ አንግቦ የሚሰራ ሳይሆን ለቆመለት ራዕይና አላማ የሚሰራ ነው። መሪ የሰዎች መሳቅ ልቡን የማያሞቀው፣ የሰዎች ወሬና አግላይነት የማያስጨንቀው በህይወት ዘመኑ ግን መሪ ለሆነበት ስራ ታማኝና ውጤታማን ስራ ሰርቶ ማለፍ የሚችል መሆን አለበት።
መሪ ከሚመራቸው ሰዎች የሚለየው መሪ ስለሆነ በሚመራው ተቋም የሚመጣው ስኬት የመጀመሪያ ደስተኛው ሲሆን፣ በተቋሙ ለሚያጋጥመው ውድቀት የመጀመሪያው ተጠያቂ መሪው ነው።
መሪ የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች
፨#ለብቻ_መተው፦ መሪ ከሚያጋጥመው አስቸጋሪ ሁኔታዎች መሐል የሰዎች ሽሽትና ለብቻ መሆን ነው። ለብቻህ የሚተዉህ ሰዎች ያጋጥሙሃል። መሪ ስትሆን በሰዎች የታጀበ ህይወት ብቻ ሳይሆን ለብቻህም የምትቆምበትም ጊዜያቶች አሉ። ለብቻህ የመተው ጊዜያቶች ያጋጥማሉ። የሰዎችን አጀብ በመፈለግ የሚኳትን መሪ ሳያስበው በሚመራቸው ሰዎች ፍላጎት ስር ለመጎዝጎዝ ችግር ተጋላጭ ይሆናል።
፨#የራሳቸውን_ፈቃድ_እንድትፈጽምላቸው በሚፈልጉ ሰዎች መከበብ፦ መሪ ከሚቸግርባቸው ሰዎች አንዱ መሪው ፍላጎታቸውን እንዲፈጽምላቸው የሚፈልጉ ሰዎች የሚፈጥሩት ሁካታ ነው። ማንኛውም መሪ የመጀመሪያው ሐላፊነቱ የሚመራውን ተቋም ውጤታማ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው። ከተቋሙ ራዕይ ውጪ የሰዎችን ፍላጎት የማድረግ ሐላፊነት የለበትም። ሁልጊዜም እንደነዚህ አይነት ሰዎች የሚፈልጉት ነገር ካልተደረገላቸው የማኩረፍና፣ የታዘዙትን ያለ መስራት ዝንባሌን ያሳያሉ።
፨#የራሳቸውን_ክልል_ፈጣሪዎች እንዲዚህ አይነት ሰዎች ተቋሙ ከተቋቋመበት አላማ ይልቅ ለራሳቸው የሚመች ሰዎችን ይሰበስባሉ። በተለያዩ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚመጡ ማፈንገጦችን ስንመለከት ሁልጊዜም ችግሩ የሚነሳው በሆነ ሐሳብ በተስማሙ ግን የተሰሰቡበትን ቤተክርስቲያን ሆነ ማንኛውም ተቋም ውስጥ ራሳቸውን የሚመስሉ ሰዎችን በመሰብሰብ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን መፍጠር ነው። ህብረት አስፈላጊ ነው ነገር ግን የተቋምን አኪያሄድ የሚጎዳ ነገር ካለው ግን ፈጥኖ መታረም ይኖርበታል። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ከሰዎች ጋር ስለተስማሙ ብቻ መሪውን እንደፈለጉ መጠምዘዝ እንደሚችሉ የሚያስቡ ናቸው።
፨ #ለሐሜት_ተጋላጭነት መሪ ሁልጊዜም ለሐሜት ተጋላጭ ነው። ሁለም ሰው አስተያየት መስጠት የሚቸኩለት መሪው ላይ ነው። መሪ ሰዎች ለሚሰጡበት አስተያየት ራሱን ማዘጋጀት አለበት። ለጥሩም ለመጥፎም። በጣም የሚገርመው መሪ ከሚያልፍባቸው መንገዶች አንዱ ይህ መሆኑ ነው። ሰዎች እነርሱ ያልሰሩትን አንተ እንዳልሰራህው ችግሩ ከአንተ እንደሆነ ሊያላክኩ ይችላሉ። ብዙ ሰው በቀላሉ አፉን የሚከፍተው በመሪዎች ላይ ነው። የፈለገ ጥሩ መሪ ብትሆንም ከሚያሙህ ሰዎች አታመልጥም።
፨#የራስን_ችግር_ወደ_መሪ_መለጠፍ፦ መሪ ስትሆን የራሳቸውን ችግር ወደ አንተ የሚያላክኩ ሰዎች ያጋጥሙሃል። አጥፍተው ስትገስጽ እነርሱ የሚታገሉትን ያጠፉትን ማረም ላይ ሳይሆን፣ መገሰጻቸው ትክክል እንዳልሆነ ያስባል። ከመሪ ሰራዎች አንዱ ተቋምን የሚጎዳ አኪያሄድ ሲመጣ መገሰጽ አልታረም ካለ በአግባቡ እርምት መውሰድ ነው። ሁልጊዜም ይህን አርሙ ሲባሉ ማረም የማይፈልጉና ችግራቸው የማይታያቸው ሰዎች የራሳቸውን ችግር ወደ አንተ በማላካክ አባዜ የተሞሉ ናቸው። ለተሰበሰቡበት ተቋም ክብር የሌላቸው ሰዎች ሁልጊዜም የሚታገሉት ስለ ራሳቸው ክብር ነው። ከዚህ የተነሳ በተቋም ውስጥ ስላለው አሰራር ግድ አይሰጣቸው።
፨#የመመራት ልብ ያጡ ግለሰቦች- ምንም አይነት እንከን አልባ መሪ ቢኖር እንኳ ሰዎች የመመራት ልብ ከሌላቸው የመሪው ብቃት ብቻ ለውጥን አያመጣም። የመመራት ልብ መታጣት ለመሪዎች ሁልጊዜም አስቸጋሪ ሆኔታ ነው። ሁሉም አዋቂ፣ ሁሉም መሪና አለቃ እንደሆነ በሚሰማው ስፍራ የመሪ መኖሩ ምንም ጥቅም የለውም። "ከበሮ ሲያዩት ያምራል ሲይዙት ያደናግራል" እንደሚባለው የመመራት ልብ የሌላቸው ሰዎች በመሪው አመራር ሁሌም አስተያት ሰጪዎች ናቸው። ግን ደግሞ እሺ እናንተ ምሩ ብላችሁ ስተሰጧቸው አበላሽተው ይጠብቁአችኃል። የመመራት ልብ ልክ መሪ የመኖሩን ያህል አስፈላጊ ነው።
......ይቀጥላል.......
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
"እውነተኛ ትህትና እግዚአብሔር ስለ ማንነታችን ከሚናገረው ጋር መስማማት ነው።"
- ዳንኤል ስትሪክላንድ
"True humility is agreeing with God about who you are."
- Danielle Strickland
#መሪ_ና_ተመሪ
አንድ ተቋም ውድቀቱ የሚጀምው መሪ አያስፈልግም ሲልና፣ መሪ ያልሆነ ሰው የመሪነት ቦታ ላይ ሲቀመጥ ነው። ዛሬ የማወራው ስለ መሪዎች ብቻ ሳይሆን ስለ ተመሪዎችና የመሪ ጥቅም ነው። መሪ ብዙ ጊዜ የሚያስፈልገን በማይመስለን ጊዜ እንኳ ሳይቀር ጠቃሚ መሆኑ ይገርማል። የቤተክርስቲያን መሪ መንፈስ ቅዱስ ቢሆንም በእነርሱ ሆኖ የሚመሩን ሰዎችን ራሱ መንፈስ ቅዱስ ይሰጣል። መሪ ማለት አገልጋይ ማለት አይደለም መሪ ማለት አለቃ ማለትም አይደለም ፤ መሪ ማለት እሱ እየመራህ የምትከተለውና በህይወትህ ልትደርስበት የሚገባህ ቦታ ላይ እንድትደርስ አኪያሄድ የሚያስተምርህ ነው። መመራትን የማይወድ ሰው መሪ መሆን አይችልም።
* መሪ ሐላፊነትን ይወስዳል
* መሪ ተጠያቂነትን ይቀበላል
* መሪ በሚፈጠሩ ችግሮች ወዲያው መፍትሄን ይጠሳል
* መሪ በንግግር ብቻ ሳይሆን በህይወት ምሳሌነት ይመራል
*መሪ የዛሬን ደስታ ሳይሆን የነገን የተሻለ ውጤት ያስባል
*መሪ እንደ ተመሪዎች አያስብም ወይም በሚመራቸው ጭንቅላት አያስብም። ያ ማለት ከሚመራቸው ሰዎች ሐሳብ አይቀበልም ወይም አይማርም ማለት አይደለም።
የብዙ ተመሪዎች ችግር መሪያቸው ለምን ያንን ነገር እንዳደረገ ከማሰብ ይልቅ መሪያቸው እንደ እነርሱ እንዲያስብ ይፈልጋሉ። መንፈሳዊ የጠረመስክ ሲመስልህ መሪህን ከገፋህ ውድቀትህ ይቀድማል። ማወራው ስለ ትክክለኛ መሪዎች እንጂ ጥቅም ፈልገው ሊገዙህ እየፈለጉ እንምራህ የሚሉትን አይጨምርም።
እግዚአብሔር መንፈሳዊ መዋቅሩን በመሪዎች ስር ማድረጉ በራሱ ያስገርማል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብዙ አገልጋዮች መሪዎችን ባለማክበር ችግር ውስጥ እንዳሉ አስባለው። ታውቃለህ በመሪህ ላይ ዘርተህ የምትሄደውን ነገር አንተ እንደምታጭደው? ግድ ነው። እውነተኛ መሪና ቅጥረኛ ወይም ሞያተኛ መሪ በአኪያሄድና በውጤታቸው ይለያሉ።
መሪ ስትሆን የሚሰጠው ውጤት ላይ እንጂ ሰዎች ዛሬ የሚያስቡት ነገር ላይ አታተኩር። መሪ ሁልጊዜም በተመሪዎቹ አህምሮ ካሰበ ህብረቱን አገልግሎቱን። ሌላው መሪ ስትሆን ትውልድ ከፊት የሚያየው አንተን ነውና ከንግግር ባለፈ በህይወት ምሳሌ መሆን አስፈላጊ ነው።
The 44th President - In His own Words የሚል የባራክ ኦባማ ዶክመንተሪ አይቻለሁ። በእርሱ ዘመን የሰራቸውን ታላላቅ ዘጠኝ ስራዎች ይተርካል። በዚህ ዶክመንተሪ ስታይ መሪነት አለቃነት ሳይሆን ሸክም መሆኑን ትረዳለህ። ባራክ ኦባማ በእነዚያ ስምንት አመታት ውስጥ ምን ያህል እንደሸበተና ፊቱ እንደገረጣ ማስተዋል ትችላለህ። በመጨረሻ ሲናገር " እኔ አሁን ዛሬ ያለ ሰዉ የሚሰጠኝን ሐሳብ ብቻ ላይ ሳይሆን ከዛሬ 30 አመት በኃላ ትውልዱ አይቶ የሚናገረውን ታሪክ ሰርቻለሁ" ብሏል። መሪ ዛሬ አንተን ለማስደሰት ሳይሆን ነገ ልትደርስበት የሚገባህን ነገር አይቶ ይሰራል።
አንዳንድ ሰዎች በተለያዩ ጸጋዎች ስላገለገሉ ብቻ መሪ መሆን የሚችሉ ይመስላቸዋል። አንዳንዶቹ በጸጋቸው መልካም ያገለግሉና ሲመሩ ግን ገደል ይከታሉ። በመሰረቱ አገልጋይ መሆን መሪ መሆን ማለት አይደለም። መሪ ሆነህ ሰባኪም ላትሆን ትችላለህ ግን ትውልድን የሚያሻግር ጥበብ አለህ ማለት እንጂ። አስቀድሞ መሪነትን ያልተሰጠውና በእግዚአብሔር መንፈስ የማይመራ መሪ ሊሆን አይገባውም። ቤተክርስቲያን የሚያስፈልጋት የሚያዘልሉ አገልጋዮች ብቻ ሳይሆን ድንቅ መሪ የሆኑ አገልጋዮችም ጭምር ነው። ማንም ሰው ያለ መሪ እንዲኖር አልተፈቀደም፣ መሪ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት እንዲመራም አልተፈቀደም። ለትውልድ የሚሰራ መሪ የግድ ያስፈልጋል።
...ይቀጥላል....
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
ስለ ራዕይና ስለ ታላቅ ህልም ከሚያወሩ ሰዎች ጋር እንጂ፣ ስለ ሰዎች ሐሜት ከሚያወሩ ጋር ጊዜህን አታሳልፍ።
/channel/theideaofs
ሐዋሪያው ዳንኤል መኮንን በፈውስ አገልግሎት እግዚአብሔር ብዙ ስራ ሰርቶበታል። ቄስ በሊና ስለ ሐዋሪያው ዳንኤል አገልግሎት እንዲህ ይላሉ ፦ " እኔ ፣ሐዋሪያው ዳንኤል መኮንንና፣ መጋቢ ዳን ስለሺ እንግሊዝ ሐገር በአንድ ኮንፍራንስ ላይ ልናገለግል ተጋበዝን። ዳንኤል መኮንን መድረኩ ላይ ሲቆም በአስገራሚ ሁኔታዎች ሰዎች ይፈወሱና በበሽታዎች ይቀልጡ ነበር" ብለውኛል። ቄስ በሊና በእርሳቸው ዘመን ካገለገሉ ሰዎች መሐል በጣም የሚወዱት ዳንኤል መኮንን እንደሆነ ነግረውኛል።
ሰዎች በተለያዩ ፀጋዎች ለቤተክርስቲያን መታነፅ ይሰጣሉ። በሐዋርያው ዳንኤል ላይ በሐይል የፈውስ ቅባት ይገለጥ ነበር። ይህ ማለት ሌላ ፀጋ አይገለጥም ነበር ለማለት አይደለም በጉባኤው ትንቢትም ይነገር ነበር።
"ኑ ፀሎትን ወደ ስፍራውን እንመልስ" የሚል የወንድም አዲስ ጌታቸው መፅሀፍ ላይ በዳንኤል መኮንን የአገልግሎት ዘመን ስለነበረው አገልግሎት በገፅ 328 ላይ፦
" አጋንንቶች ከቤተክርስቲያኒቱ አምስት መቶ ሜትር ርቀት ላይ ሳሉ ይጮሁ ነበር" ይላል። ሌላው ደግሞ በጣም የሚገርመው ብዙዎቹ አዳዲሶች እያለቀሱ ጌታን ይቀበሉ ነበር ብዙ ነፍሳት ይጨመሩ ነበር። ብዙዎቹ ግን በጣም የሚስማሙት ዳንኤል መኮንን ላይ ሐይለኛ የፈውስ ፀጋ ይገለጥ እንደነበር ነበር።
አንድ የእግዚአብሔር ሰው "እርሱ እንደውም የፈውስ ሐዋሪያ ሊባል የሚገባው ነው" ብሎኛል። በዳንኤል መኮንን የአገልግሎት ታሪክ ውስጥ በፈውስ አገልግሎት ትልቅ ስራ እግዚአብሔር ሰርቷል። ክብር ለኢየሱስ ይሁን።
የኦሎንፒያ መሰረት ክርስቶስ ሪቫይቫል
የኦሎንፒያ መሰረተ ክርስቶስ ሪቫይቫል ብዙዎች ከእስራት የተፈቱበት፣ ብዙዎች የተፈወሩበት፣ ብዙዎች አገልጋዮች የተነሱበት ታላቅ ሪቫይቫል ነው። እግዚአብሔር በስራ ላይ ነበር። ብዙዎች ከተለያዩ እስራት ተፈውሰዋል። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን። ሐዋሪያው ዳንኤል ከኦሎንፒያ ሪቫይቫል በተጨማሪ በአሜሪካ ያለችውን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያን ተክለዋል፣ ከዚያም ወደ አገራቸው ተመልሰው የወንጌል ብርሃንን ቤተክርስቲያን ተክለዋል። ከወጣትነት ዘመን ጀምሮ እስከ ሽምግልና እግዚአብሔር ስለሰራባቸው ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን። የኢትዮጵያ አብያተክርስቲያናት ስላገለገሉ እኛም እናመሰግናለን። ይህች ታሪክ ለመነሻ ለማስታወስ ያህል ናት። የህይወት ታሪካቸው ተጽፎ እንደምናነብ ሙሉ እምነት አለኝ።
አሁንም እግዚአብሔር በስራ ላይ ነው። ታሪክ አንባቢ ብቻ ሳንሆን ታሪክ ሰርተን ወንጌልን ለትውልድ እናሻግራለን።
#ሪቫይቫል_በእኛም_ዘመን_ይቀጥላል!!
( ይህን ጽሑፍ ጽፌ በፌስ ቡኬ ላይ ያጋራሁት በ 2017 ነበር። በተለያዩ መንገዶች ሰዎችን ጠይቄ ካገኘሁት መረጃ ሌላ አንዳንድ መረጃ ያገኘሁት ከወንድም አዲስ ጌታቸው 'ኑ ጸሎትን ወደ ስፍራው እንመልስ' ከሚለው መጽሐፍ ነው።)
/channel/theideaofs
#የፌሚኒዝም_አቀንቃኝ_ፌሚኒስቶች
ወደ ቲክቶክ መንደር ወይም ወደ ተለያዩ የማህበራዊ ድረ-ገጾች ገባ ስትሉ "ፌሚኒዝምን" የሚያቀነቅኑ 'ፌሚኒስት' ወጣት ሴቶችን ማየቱ እየተለመደ ነው። ፌሚኒዝም በአገራችን ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ እየታየ ያለ ክስተት ቢሆንም፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ እንዲሁም በሌሎች አገራት ለአባት-አልባ ህጻናት (Fatherless Children's) እንዲሁም ባል-አልባ ሴቶች መብዛት ምክንያት የሆነ ከመሆኑም በላይ በዚህ አይነት መንፈስ የተያዙ ሴቶች በብዛት ወንድ-ጠሎች እና ለተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ሰለባዎች ናቸው።
መነሻ ሐሳቡ የሴቶችን ከወንድ "እኩልነት" ያድርግ እንጂ በዚህ አሳቤ የተያዙ 'አንዳንድ' ሴቶች ከመጠን ባለፈ ራስ-ወዳድነት (Self-love) የተያዙ እና ከማንም አናንስም በሚል የበላይነት-አቀንቃኝነት መንፈስ ተጠቂዎች ናቸው።
አብዛኞቹ የጀርባ ታሪክ ያላቸው ናቸው
ለሁሉም መነሻቸው ይህ ላይሆን ቢችልም አብዛኞቹ ፌሚኒስት ሴቶች በወንድ የተጓዱ፣ በቅርብ የቤተሰብ አካል በሆነ ሰው ጥቃት የደረሰባቸው፤ ወይም ደግሞ በሚያውቋት ሴት ወይም የቅርባቸው በሆነች ሴት የደረሰን ጥቃት የሚያውቁ ሴቶች ናቸው። አብዛኛው የፌሚኒዝም አቀንቃኝነት ከጥቃት የተወለደ ሲሆን፣ ጥቂቱ እኩል ነን ከሚል እሳቤ ከሚወለድ ተዛማጅ ጉዳይ ነው።
ራሳቸውን የቻሉ (Independent) ሴቶች
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ቀደም ባሉ አመታት ሴቶች ሙሉ በሚባል ደረጃ ሴቶች የወንዶች ጥገኛ በመሆናቸው ህይወታቸው በአጠቃላይ በወንዶች ተጽዕኖ ስር ነው ያ ደግሞ ለብዙ ጥቃት እንዳጋለጣቸው ያምናሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቶች በስራ እና በቢዝነስ ራሳቸውን መቻላቸው ሴቶች ከወንድ በምንም አያንሱም እኩል ነን እኛም እንችላለን ብለው ያምናሉ። ያ በራሱ ምንም ችግር ባይኖረውም ራስን- የቻለች ሴት መሆን ማለት ከወንድ በላይ እንደሆነች ለማሳየት ሳይሆን ህይወትን በተሻለ ለመምራት ነው። ራስን መቻል እጅግ አስፈላጊና መሆን ያለበት ቢሆንም ግለኛ-ንግስት በመሆን ከጤናማ ህይወት ወቶ ለመኖር ምክንያት መፍጠሪያ አቅም መሆን የለበትም።
አደጋዎቹ
፨ ትዳር-ጠል መሆን፦ ፌሚኒስት ሆና አግብታ በስርአት ትዳር የምትመራ ሴት ማግኘት እጅግ ከባድ ነው። ትዳር ጠል መሆን እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን በረከት መግፋት ነው።
፨ ወንዶችን መናቅ- ፌሚኒስት የሆኑ ሴቶች ወንዶችን የመናቅ ዝንባሌንና የፈለጉትን በወንዶች ላይ የማድረግ ፍላጎት ይታይባቸዋል። የዚህ አደጋ ደግሞ አንድን ወንድ ባል ብላ ተቀብላ ለመኖር አትችልም። ሴቶች ከወንድ በታች አይደሉም ብለው የሚያስቡ ግን ደግሞ እነርሱ ከወንድ በላይ እንደሆኑ የሚያስቡ ሴቶች ማለት ነው።
፨ ነጠላ-እናትነት (Single Mom)
ሴቶች በአባቶች እንዝላልነት፣ በአባቶች ችግር ወይም በመለያየት እና በሞት ጭምር ነጠላ እናት ሊሆኑ ይችላል ይህ እነዚህን አይጨምርም። ፈልነውና አቅደው ከአንድ ወልደው ለብቻቸው እናት በመሆን የማሳደግ ዝንባሌ ማለት ነው። ይህ አይነት አመለካከት የሚወለደው ከፌሚኒዝም ጽንሰ-ሐሳብ ነው።
፨ ከተፈጥሮ ጋር መጋጨት- ይህ አይነት አመለካከት ያላቸው ሴቶች ግብረስጋ ግንኙነትን ለመዝናናት- የተሰጣቸውን ሴትነት እንደፈለጉት ለመሆን ይጠቀሙበታል። ሴት ልጅ በተፈጥሮዋ በማንነትዋ ለልጆችዋ ምሳሌ የሆነች እናት፣ ለባልዋ ምርጥ ሚስት፣ በማህበረሰቡ መካከል ታላቅ ሴት የመሆን በተፈጥሮ የተሰጣት አቅም አላት። የፌሚኒዝም አመለካከት ችግሩ ሴት ከተፈጠረችበት አላማ ውጪ ያኖራታል። ነጠላ-እናትነት ብቻ ሳይሆን መውለድ ሳይፈልጉ እንደፈለጉት እየሆኑ መኖርን እንደ አማራጭ መያዝንም ይጨምራል።
፨ ከፈጣሪቸው ጋር ያጋጫታል- ሴትነትት ሆነ ወንድነትን ሰዎች ፈልገውት የተሰጣቸው አይደለም ፈጣሪያቸው የሰጣቸው ነው። እርሱ ደግሞ እኛም የፈጠረበት ማንነት አለው። እግዚአብሔርን የምናከብረው እርሱ ለፈጠረን አላማ መኖር ስንችል ነው።
እንግዲህ ይህን በጥቂቱ ካልኩ ለመፍትሄ ከሆነኝ ሁለት ችግሮችን ሳልነካ ማለፍ አልፈልግም። የመጀመሪው በሴቶች ላይ ያለ አለ-አግባብ የሆነ ጫና እና የስነ-ልቦና ጥቃት፣ ሲሆን ሌላው ደግሞ 'የዘመናዊነት' ነጻ እሳቤ ናቸው።
፨ የስነ-ልቦናና የጾታ-ጥቃት፦ ሴቶችን የበታች በማድረግ የስነ ልቦናና ጥቃት ማድረስ ከቤተሰብ ጀምሮ፣ የጾታ ጥቃት በማንኛውም ወንድ በቤተሰብ ውስጥ ወይም ውጪ መቆም ያስፈልገዋል። ለዚህ ደግሞ የአብዛኞቹ ወንዶች አኪያሄድ መታረም ያለበት ነገር ነው። ለዚህ አለም ህይወት የሴት ልጆች ሚና ከፍተኛ ነው ያ ደግሞ የተወሰነው በፈጠረን አምላክ ነው። ሴቶችን ለፍትወት ብቻ እንደተፈጠሩ ማሰብ እስካላቅምንና፣ እንደ ቤት ሰራተኛ አገልጋይ 'ብቻ' ማሰብ እስካላቆምን ድረስ ብዙ ሴት እህቶቻችን አሁን ወደ ምድራችን እየተነዳ ወዳለው ከፌሚኒዝም- ጎርፍ መታደግ አንችልም። ከላይ ለማለት እንደሞከርኩት ሁሉም ፌሚኒስቶች የጥቃት ሰለባ ባይሆኑም አብዛኞቹ በህይወታቸው ከደረሰ ወይም በሌላ ሲደርስ ካዩት የመጣ ጥላቻ ምክንያት ነው።
፨ የዘመናዊ ነን ተጠቂዎች? ፌማኒስት ነኝ የሚሉ ሴቶች በሙሉ ዘመናነዊ ነኝ! ነጻ ነኝ! በሚል ህይወት የተያዙ ናቸው። ዘመናዊ የሆነች ሴትና ነጻ የሆነች ሴት መሆን ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ ከጤናማው የሴት ልጅ ያፈነገጠ ህይወትን ከተከተልን ምኑን ዘመነው? የእኩልነት ጥያቄ ሴቶች ሲያነሱ አንሰናል እያሉ እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው። የሁለቱም አካላት ሚና የተለያዩ ናቸው። ሁለቱም መቀያየር አይችሉም ያን ደግሞ እንደዚህ አድርጎ የፈጠረው እግዚአብሔር ነው። ዘመናዊነት ህይወት ቀላልና በተሻለ እሳቤ ለመምራት ነው። ተፈጥሮናንና የእግዚአብሔር የጋብቻና ንጹህ የሆነ የህይወት አኪያሄድን የሚቃረን መሆን የለበትም። ዘመናዊ ሴት መሆን ማለት ትክክለኛ ትዳር ለመመስረት እውቀት ያላት፣ ብቃት ያላት ማለት ነው።
በመጨረሻም- በዚህ አቅጣጫ በተጠናከረ ጥናታዊ ጽሑፎችን አካትቼ የምመለስ ይሆናል። የወንዶችንና የቤተሰብን፣ የማህበረሰብን ለዚህ አጋላጭ የሆኑ ችግሮችንም እናያለን።
ነገር ግን ሴት እህቶቻችንና፣ ታዳጊ ሴት ልጆቻችንን ከዚህ ሚዛኑን ከሳተ አመለካከት በእውቀት መጠበቅ እጅግ ያስፈልጋል።
(በዚህ ጽሑፌ ጤናማ ህይወት የምለው- ትዳር መስርተው፣ ልጆች ወልደው፣ ለባሎቻቸው ሚስት፣ ለልጆቻቸው መልካም እናት መሆን የሚችሉ ማለቴ ነው።)
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
የሰሞኑን መነጋገሪያ የሆነው የ Asbury University የተነሳው መንፈሳዊ ንቅናቄ በስፋት እየተመለከትን ነው። በዚህ መንፈስ ብዙዎች እየተነኩ እና እግዚአብሔርን እየፈለጉ እያየን ነው። September 2, 1890 የተጀመረው ይህ ዩንቨርስቲ እስከ አሁን እያስተማረ ይገኛል። የመጀመሪያ ከ 1890-1991 ድረስ Kentucky Holiness College ከ 1891-2010 Asbury College የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ አስበሪ ዩንቨርስቲ እንደሚባል Wikipedia ይነግረናል።
በ 1970 በዚሁ ኮሌጅ ይህ አይነቱ ሪቫይቫል ተከስቶ ነበር። እግዚአብሔር አምላክ በመንፈሱ ብዙ ወጣቶችን ለአገልግሎት አዘጋጅቷል አነቃቅቷልም። በዚያ ውስጥ ብዙዎች ተፈውሰዋል። ብዙዎች ተለውጠዋልም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችና፣ በኮሌጆች ደረጃ እንደዚህ አይነት መንፈሳዊ መነቃቃትና ሪቫይቫል ሲነሳ ብዙ ወጣቶችን ለመንፈሳዊ አላማ አቅም የማስታጠቅና የማነሳሳት እንዲሁም ወደ ብዙ ትውልድ የመወራረስ አቅሙ ከፍተኛ ነው። እኛ ሐገር ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ከዚህ ተሞክሮ የሚወስዱት ነገር ይኖራል ብዬ አምናለሁ። በመንፈሳዊ ትምህርቶች ቤቶች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ከማስተማር በተጨማሪ መጸለይና በስፋት እግዚአብሔር ማምለክ በስፋት መዳበር ያለበት ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶቻችን መንፈሳዊ ሰዎችንና አገልጋዮችን የምናወጣባቸውና ስፍራ መሆን አለባቸው።
#ቸኩሎ_መፍረድ
"ሰዎች ላይ የምትፈርድ ከሆነ፥ ሰዎችን ለማፍቀር ጊዜ የለህም።" ማዘር ትሬዛ
ሁላችንም ጋር በተለያየ መንገድ የሚያጋጥመን ወይም አሁን እያደረግነው ያለነው ሊሆን ይችላል የምናደርገው ነገር ቸኩሎ መፍረድ እና ሰዎችን በሆነ ቦታ መመደብ ነው።
ሰዎችን ሳናውቃቸው ስለ እነርሱ ያለን የተሳሳተ ሐሳብ፥ እያለፉበት ያሉት ትግላቸውን (Struggle) ሳንረዳ እንዲህ ነው ብለን የምንፈርደው ፍርድ፥ ገና ሳየው አይመቸኝም ብለን ከሰውየው ማንነት በተለየ ሌላ ያንን ሰው በውስጣችን ፈጥረን እንዲህ ነው ብለን ወስነን የምንኖር ስንቶቻችን እንሆን? በህይወታችን አደገኛው ነገር ቸኩሎ መፍረድ ነው።
አንድ አሁን ጓደኛዬና ወዳጄ የሆነ አገልጋይ አለ። እንዲህ ከመቀራረባችን በፊት ስለ እርሱ የነበረኝ ግምት ገና ሳላውቀው የተሳሳተ ነበር። ጉረኛ፥ አፈር አይንካኝ የሚል አይነት አድርጌ አስበውና በአህምሮዬ 'እንዲህ ነው እሱ' ብዬ ደምድሜ ነበር። ስቀርበው ግን ከህይወት እና ከባህሪው ብዙ የምማርበት ምርጥ ወዳጄ ሆነኝ።
ሰዎችን የህይወታቸውን መንገድ፥ አንድን ነገር ያደረጉበትን ምክንያት፥ የህይወታቸውን ትግል ጭምር ቀርቦ መረዳት ያስፈልናል። ስንቶቻችን ስለ ማናውቃቸው ሰዎች እና ስላልተረዳነው ጉዳይ 'እንዲህ እኮ ነው' ብለን ፈርደን፥ ወስነን ደምድመን ይሆን? ድሮም ፍርድ ለሰው ልጆች አልተሰጠም ለሚቀርበንና ለምንፈልገው እኛ የፈለግነውን መልካም ፍርድ ስንሰጥ፥ ከእኛ ጋር ቅርበት ለሌለው ደግሞ የተሳሳተ ፍርድ ስንፈርድ እንገኛለን። ቸኩሎ ለመፍረድ ምንም እውቀት አያስፈልገውም፥ ነገሮችን መዝኖና አስተውሎ ማድረግ ግን ጥበብ ነው።
ሰዎችን ለማወቅ፥ ለመረዳት እና ለማገዝ እድል እንስጥ!!
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
ካመለጡህ ሶስት ነገሮች መመለስ የማትችላቸው ነገሮች፦
ጊዜ (Time)
ንግግሮችን (Words)
ዕድል ወይም አጋጣሚዎች (Opportunity)
፨ጊዜህን በአግባብ ተጠቀምበት (ጊዜ ተመልሶ የማይገኝ ዕንቁ ነው)
፨ ንግግርህን አስበህ ተናገር (የአፍ ወለሞታ በቅቤ አይታቅምና)
፨ የተሰጡህን አጋጣሚዎች በአግባቡ ተጠቀምባቸው
(የጠቢባን ምክር)
/channel/theideaofs
ነገራችን ወሬ ብቻ እንዳይሆን!
“ስለ አንድ ነገር የምታወሩ ከሆነ ነገሩ ህልም ይባላል፣ ስለነገሩ በሚገባ ማሰብ ስትጀምሩ ነገሩ ወደመቻል ይሸጋገራል ማለት ነው፣ ለነገሩ የጊዜ ሰሌዳ ካዘጋጃችሁለት ግን ነገሩ እውን ወደመሆን ይመጣል” - ANTHONY ROBBINS
• ቁጭ ብላችሁ ወደማሰብና ስለነገሩ ወደማሰላሰል ያልደረሰ እስካሁን በወሬ ብቻ የቀረውን ነገር እስቲ ለማስታወስ ሞክሩ!
• ካሰባችሁና ካሰላሰላችሁት በኋላ ወደ እርምጃ እና ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት የጊዜ ገደብና ሰሌዳ ያላስቀመጣችሁለትንም ነገር እስቲ አስቡት!
ነገሮቻችሁ ከወሬ አልፈው ሃሳባችሁን እንዲገዙት፣ ከሃሳብ አልፈው ደግሞ ወደ እውነታ እንዲመጡ ከፈለጋችሁ ይህንን መርህ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡
ንግግራችን ረገብ፣ ሃሳባችሁን ሰፋ፣ እቅዳችሁ ደግሞ ተግባራዊ በማድረግ ልቃችሁ ተገኙ!
ዶክተር ኢዮብ ማሞ
#የስሜት_ብልህነት እና #ስሜት_ያለቦታው
የስሜት ብልህነት ( የስሜት መብሰል) ለዚህ ዘመን ትውልድ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። ስሜት ያለቦታው፣ የስሜት ስስነት፣ የስሜት መዘበራረቅ፣ የተጋነነ ስሜታዊነት ወይም ስሜትን መቆጣጠር አለመቻል በመጥፎም ጎኑ በጥሩም ጎኑ በስፋት የሚታይበት ጊዜ ላይ ነው። ስሜት በተገቢው ቦታና በተገቢው ሁኔታ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ነው። የማህበራዊ ድረ-ገጾች መብዛት ትውልዱን በስሜት ልቅነት፣ እንደፈለገው የመናገር አባዜ ያንንም እንደ ነጻነት የመቁጠር ተጨማሪ አባዜ፤ መንፈሳዊ ማህበራዊና ተፈጥሮአዊ ግብረ-ገብነትን የማጣት የበዛ አባዜ ውስጥ እየተገባ ነው።
በስሜት በየማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ እንደፈለገው ሲሳደብና ሰዎችን በማዋረድ የሚታወቀው እንደ ዮኒ ማኛ ያለ ሰው ስለ ስሜት-ብልህነት ቲቪ ላይ ቀርቦ ትምህርት ሲሰጥ ከማየት የበለጠ ችግር አለ? ጊዜው የበሰሉና አገር ያቀኑ ቀዳሚ ሰዎች የማይሰሙበት፣ አባትና እና በማይከበሩበት ቦታ ራስን መግዛት ከየት ይመጣል።
ቶሎ ተስፋ መቁረጥ፣ አኩሪፊነት፣ ግልፍተኝነት፣ ጸብ አጫሪነት፣ አሉታዊ በሆነ መልኩ ደግሞ ወዲያው ሰው አማኝነት፣ አፍቃሪነት፣ ደጋፊነት ስሜትን በምክንያት ያለመምራት ችግሮች ናቸው። ሰው ስሜት ብቻ አልተሰጠው ፈቃድና እውቀት አለው። ስሜት ከእውቀት ውጪ ሲሆንና ከፈቃድህ ቀድሞ ከመራህ ሁልጊዜም አደገኛ ችግር ነው። ራሳችን ላይ የስሜት ብልህነት ላይ አትኩሮ መስራት እጅግ ያስፈልጋል። ስሜትን በብልሃት ከመምራት አንጻር እኔን የጠቀሙኝን ጠቃሚ ሐሳቦች ላጋራችሁ።
#ነገሮችን_ማሳለፍ፦ ስሜት በተለያዩ ምክንያቶች ሊያስቆጣን ወይም ያልተገባ ውሳኔን ለመወሰን ወደ መውሰድ ከመምጣቱ በፊት የተፈጠረውን ነገር ታግሰን እንዲያልፍ ማድረግ መቻልን መልመድ አለብን። ይህን መርህ ጭንቅላትን ማቀዝቀዝ እለዋለሁ። አህምሮችን በስሜት ተነድቶ ያልተገባ ከመደረጉ በፊት ማረጋጋት ማለት ነው። ነገሩ ሲያልፍ ከስሜታዊነት ወተን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ነገሩን ማስተዋል እንችላለን።
#ንግግር_አለማብዛት፦ ስሜት በጋለ ወቅት ንግግር ማብዛት ማለት እንደገነፈለ ወተት መሆን ማለት ነው። ከዚያ ይልቅ ንግግርን መቀነስ እጅግ ያስፈልጋል። ስሜት ሲግል በቁጣ ወይም በደስታ ሰው የሚያወራውን አያውቅም። ልባችን በተጎዳና ስሜታችን በተነካ ጊዜ ከጉዳዩ ጋር የሚያገናኘው ጋር ሰው ጋር ሰላማዊ ምልልስ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ከሰዎቹ ጋር ቀጣይ ዘመን አብሮ ለመሔድ ባዘንባቸው ጊዜ ስሜታችን ፈንድቶ ንግግራችን ጉዳይ እንዳያመጣ ንግግርን መግታት ያስፈልጋል።
እነዚህን ሁለት ነጥቦች ካልኩ ይበቃል። ሁላችንም እየተማርን እየበስልን እንሄዳለን።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#መጋቢ_በቀለ_ወልደ_ኪዳን "#ተንቀሳቃሽ_መፅሐፍት_ቤት (#Library)"
"ነቢያትና ለግል የሆነ ትንቢት" የተሰኘውና በዶክተር ቢል ሐሞን ተጽፎ በመጋቢ በቀለ ወልደኪዳን የተተረጎመው መጽሐፍ ሲመረቅ አንድ አገልጋይ ስለ ጋሽ በቄ ሲናገር "The walking Bible" እንዳለው አስታውሳለሁ።
በአንድ ወቅት ( ይህ ታሪክ የሆነው በ2011 ነው) መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን መፅሐፍ ለሰው ሊሰጥ አብረን ቤቱ ይዞኝ ሄደ ። አብራን አንዲት አገልጋይ እህትም አብራን ነበረን። ቤቱን ለመጎብኘት ባንሄድም ልክ፣ እኔም ቤቱ ስሄድ የመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም በውስጤ ግን ማየት የምፈልገው ነገር ነበረኝ። መፅሐፎቹን። "ከህንፀት" መፅሔት ጋር ባደረገው ሰፊ ቃለ መጠይቅ ስለ መፅሐፎቹና ብዛትና ስለ አንባቢነቱ ተጠይቆ የመለሰውን አንብቤ ነበርና መፅሐፎቹን ለማየት እጅግ ጓጓሁ።
ገና ወደ ቤቱ ስንገባ በበሩ በስተ ግራ አነስ ያለች መደርደሪያ ላይ የተወሰኑ መፅሐፍቶችን አየሁና በውስጤ ያ ብዙ የተነገረለት የቤት-ላይብረሪ ይህ እንዳልሆነ ገመትኩ ። "ጋሽ በቄ መፅሐፍቶችህን ማየት እፈልጋለሁ" አልኩት። እርሱም "ብዙ መፅሐፍት እኮ የለኝም" አለኝ። እዛው ክፍል በስተ ቀን ወንበር ላይ ቦታ አተው የተቀመጡ መፅሐፍት አየሁ።
"ጋሽ በቄ የመፅሐፍት ክፍልህን አሳየኝ" አልኩት እርሱም ወደ መኝታ ክፍሉ መራኝ። ወደ ክፍሉ እንደገባሁ በስተ ቀኝ በግርግዳው ጋር የተለጠፈ ትልቅ የመፅሐፍ መደርደሪያ አገኘሁ። በዚያ ክፍል ውስጥም ቦታ አተው ወንበር ላይ የተደረደሩ መፅሐፍትን አይቻለሁ። በትልቁ መፅሐፍት መደርደሪያ ላይ በጣም ብዙና በሺዎች የሚቆጠሩ መፅሐፍት ተደርድረዋል። በጣም የገረመኝ መፅሐፍቶች መኖሩ ብቻ ሳይሆን የገረመኝ ሁሉንም ማንበቡ ነው።
"ጋሽ በቄ ሁሉንም አንብበሃቸዋል?" ብዬ ስጠይቀው "ደጋግሜ ወጥቻቸዋለሁ" ብሎኛል። ያለ ማጋነን አገልጋይ ሆኖ በዛ ላይ አንባቢ እንደ ጋሽ በቄ እስከ አሁን አላጋጠመኝም። በዚህም ብዙዎች እንደሚስማሙ አምናለሁ። አንድ ሰው እንዳለኝ "ጋሽ በቄን ተንቀሳቃሽ መፅሐፍ ቅዱስ (ላይብረሪ) ነው" እንበለውን?
"እነዚህን ሁሉ መፅሐፍት ከመቼ ጀምረህ አሰባሰብካቸው?" ብለው " ተቀጥሬ ደሞዝ መብላት የጀመርኩት በ1956 ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መፅሐፍ እገዛለሁ አነባለሁም" ብሎኛል። ጋሽ በቄ በፈለግነው ሐሳብ ላይ ብናወራ መልስ ይሰጠናል። ጋሽ በቄ የማንበብ ልምዱ ይገርማል። በጣም ያነባል አሁንም ያነባል።
በጋሽ በቄ የንባብ ህይወት ብዙ ልንማር እንችላለን። አገልጋዮን ማንበብ የህይወታቸው አንድ አካል መሆን አለበት። ያላነበብነውን አናስተምርም፤ ያላወቅነውን አንኖርም። ማንበብን ልናዳብር ይገባል። የሩቅ ዘመን ተጓዥ አገልጋይ ለመሆን ማንበብ አለብን። ማሰብ የምችለው በተረዳነው ልክ ነው የምንረዳው ደግሞ ባነበብነው ልክ ነው። የጋሽ በቄን ያህል የመፅሐፍ ክምችት ባይኖረን እንኳ ያለንን መፅሐፍ ማንበብ፤ ምንም መፅሐፍ ባይኖረን እንኳ መፅሐፍ ቅዱሳችንን በደንብ ማንበብ አለብን ዋናችን መፅሀፍ ቅዱሳችን ነውና።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#የትኩረት_ናፋቂነት_ሱስ (በሽታ)
The great Comeback የተባለለት በዚህም ሳምንት የተለቀቀው የ Chris Rock "Selective Outrage" በተሰኘው ስታንድአፕ ኮመዲ ካነሳቸው ከብዙ ሐሳቦች አንጻር በስፋት መነጋገሪያ ሆኗል። በኮሚዲ ስራው መሐል " በአሜሪካ ትልቁ ሱስ ትኩረት የመፈለግ ሱስ (the addiction of attention) ነው" ይለናል። ይህ መልዕክት አሁን ያለውን ትውልድ ቅልብጭ አድርጎ ያሳያል።
ሰዎች በአካል እንወድሃለን ከሚሉን ይልቅ በየፌስ ቡክና ማህበራዊ ሚዲያዎች ፎቶአችን ላይ በሚያደርጉት react ላይክና ኮሜንት ሱስ ውስጥ ገብተናል። የሰዎችን ትኩረት የመፈለግ ከልክ ያለፈ ፍላጎት (ሱስ) ውስጥ ተጠምዷል። አንድ ፎቶ በፌስ ቡክ ወይም በኢንስታግራም ላይ ለጥፈን አስሬ እየገባን ላይክ የምንቆጥርና🤔🙄😀😂 በብዛት ላይክ ካልተደረገ ልባችን የሚወርድ ስንቶቻችን እንደሆንን ራሳችንን እናውቃለን።
ማህበራዊ ሚዲያዎች ከመጡ በኃላ ሰዎች ከሰዎች ላይክና ኮሜንት ሆኗል ያንን ክሪስ ሮክ ትኩረት የመፈለግ ሱስ ይለዋል። ስነ ልቦናችን ሰዎች በብዛት ላይክ ካደረጉት እንደተወደድን የምናስብ ካልተደረገ ደግሞ ራሳችንን የምናጣጥል ማንነታችንን በሰዎች ላይክና ኮሜንት የምንመዝን ትውልድ የበዛበት የትኩረት ናፋቂነት በሽታ የተስፋፋበት ዘመን ላይ ነን። ከልክ ያለፈ ትኩረት ናፋቂነት ሱስ ብቻ ሳይሆን በሽታም ነው።
በዚህ ዘመን ብዙ ወጣቶች በዚህ በሽታ ተጠቂ ናቸው። ራሳቸውን የሚቀበሉት ሰዎች በሚሰጧቸው ኮሜንት ላይ፣ ማንነታቸውን የገነቡት በሰዎች ላይክ ብዛት ላይ ነው። ከዚህ ሱስ ለመውጣት ራሳችንን ወደ ራሳችን ማየትና ራስን መቀበል ላይ መሆን አለበት። ከልክ ያለፈ ትኩረት ናፋቂነት በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል ምንጩ ግን ራስን በልክ አለመቀበልና፣ ደስታንና በራስ መተማመንን ሰዎች በሚሰጡን አስተያየት ላይ የመመስረት አባዜ ነው። ህይወት ከሰዎች አስተያየት፣ ማንነት ከሰዎች አድናቆት በላይ ነው።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#በይቅርታ_የሚገኝ_ፈውስ (ራስህን ይቅር በል)
በክፍል አንድ 'በይቅርታ የሚገኝ ፈውስ' ጽሑፍ ላይ ሌሎችን ይቅር ስለማለት በጥቂቱ ለማየት ሞክረናል። ዛሬ ደግሞ በይቅርታ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘውን "ራስን ይቅር ስለማለት" እናያለን።
በመጀመሪያ ማወቅ ያለብን ነገር የማንበድል፤ የማንሳሳት ሰዎች አይደለንም። "ስህተት (መሳሳት) የሰው ልጆች (መሳት አላልኩም) የተለመደ ማንነት ነው።" በሌላ አባባል "ከማይሳሳት ሰው ጠብቀኝ፤ ስህተትን ከሚደጋግም ሰው ጠብቀኝ።" እንደሚባለው ማለት ነው። ሰው ሰው ከሆነ ያለ ስህተት አይኖርም፣ ችግር የሚሆነው ስህተትን አዳብሮ ወደ ማሳት ሲመጣ ነው። በመሳሳት መሐል እግዚአብሔርን መበደል፤ ሰውን መበደል አለ። እንዲህ ሲሆን ራስን መኮነን፤ ራስ ላይ መፍረድ፤ ስለተሳሳትን ራስን እንደማንችልና ተስፋ እንደሌለው ማሰብ ወዘተ የመሳሰሉ ስሜቶች ይይዙናል። የምንወደውን ሰው ስንበድል፤ ወይም ከእኛ የተነሳ ሰዎች ሲጎዱ፤ ራሳችንም ባልተገባ መንገድ ላይ ስናገኘው፤ የበደልናቸው ሰዎች ይቅር ብለውን እንኳ ራሳችን ይቅር ማለት ሊያቅተን ይችላል።
ጸጸት፤ የበደለኞነት ስሜት፤ በራስ መተማመን ማጣት፤ ራስን መቀበል አለመቻል ወዘተ ራስን ይቅር ማለት አለመቻል ነው። ሁልጊዜም ራስን ይቅር ማለትን መለማመድ አለብን። ለዚህም ሶስት ነገሮችን ማድረግ መልካም አስፈላጊ ነው።
፨#የእግዚአብሔርን_ይቅር_ባይነት_መረዳት፦
ኢየሱስን ስንቀበል ይቅር ያልተባለልን ሐጢያት የለም። መጽሐፍ ቅዱስ፦
“ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።”
— 1ኛ ቆሮንቶስ 6፥11
ሐዋሪያው ጳውሎስ ከላይ የነበረብንን ማንነት ከነገረን በኃላ በቁጥር 11 ላይ ያለውን ማንነታችንን ይነግረናል። ታጥባችኃል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኃል። ማለትንም ይቅር ተብለናል። (We are forgiven) ስለዚህ ኢየሱስ በደሙ አንጽቶና ቀድሶ ልጁ አድርጎን ሳለ የቀደሙ ድካሞቻችንን ሰይጣን ወይም ሰዎች ወይም ራሳችን እያስታወሰን ስንወቀስ ከኖርን የእግዚአብሔርን ፍቅርና ምህረት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቃል እውነት አልተረዳንም ማለት ነው። ይቅር ተብለናል እንደ አዲስ ማንነታችን ተሰቶናል ማለት ነው። ይቅር ስለተባልን ራሳችንን ይቅር ማለትን እንማር።
#በደሎቻችንን_በንስሃ መዝጋት፦ ጌታን ካወቅንበት ጊዜ በኃላ ደግሞ የተለያዩ በደሎችን ልንበድል፣ እግዚአብሔር ልናሳዝን፣ ሰዎችንም ልንጎዳ እንችላለን። አንዳንድ ሐጢያቶች ወይም ስህተቶች ባለማወቅ፤ አንዳንዶቹን አቅም በማጣት እናደርጋለን እነዚህን በተመለከተ ማስተካከል ያለብንን ማስተካከል ማለትንም እግዚአብሔር በበደልንበት ንሰሃ ( መመለስን እርምትን) ሰውን በበደልንበት ይቅርታ በመጠየቅ ደግሞም አለመበደልን፤ በራሳችንም በሐጢያት ተገኝተን ከሆነ ንስሐ በመግባት (ሐጢያት ከማንም በላይ ራስን ይጎዳልና) በወደቅንበት ጉዳይ ንስሃንና መንገድ ማስተካከልን ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይህንን ስናደርግ ይቅር ተብለናል። ይቅር በተባልንበት ይቅር መባል ራሳችንን መቀበልን መልመድ አለብን።
#ንስሃ_በገባንበት_ነገር_እግዚአብሔር ይቅርታ አድርጎ በተቀበለን ደረጃ ራሳችንን መቀበል አስፈላኒ ነው። ይህ ነው "ለራስ ይቅርታ ማድረግ" የሚባለው። አጥፍተን ስንታረም፤ ንስሃ ስንገባ እግዚአብሔር ይቀበለናል ይቅርም ይለናል። በዛ መንገድ መልሰን እስካልተገኘን ድረስ እግዚአብሔር ይቅር ሲለን በቃ ምንም እንዳልነበረ አድርጎ ስለሆነ ይቅር የሚለን፤ ራሳችንን በዛው ልክ መቀበልን መልመድ አለብን። ራስን ይቅር ለማለት ይቅር የተባልንበት እውነታና፣ ይቅር ስንባል ምን አይነት እግዚአብሔር እንደሰጠን የእግዚአብሔር ቃል በማጥናት ማወቅ አስፈላጊ ነው።
#ይቅር_ተብለናል። (We are Forgiven)
®ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#በይቅርታ_የሚገኝ_ፈውስ!
" እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን"
ማቴዎስ 6:12
ይቅርታ የምናደርገው ለበደለን ሰው፥ ያቆሰልንን፤ ያሳዘነንን ፤ የከዳንን፤ ያማንን፤ ስማችንን በክፋ ያጠፋውን ሰው እኮ ነው? ይቻል ይሆን እግዚአብሔርስ ከአቅማችን በላይ እየፈተነንስ ይሆን? ምክንያቱም ይቅርታ ማድረግ ቃል ብቻ ሳይሆን ድርጊትም ዝግጅትም ይፈልጋልና።
በቃላቸው "ይቅርታ አድርጌለታለው " የሚሉ ሰዎችን እኔ በግሌ አላምንም፡፡ ይቅርታ እኮ ብዙ ትግል፤ ትልቅ ውሳኔ ይጠይቃልና።
እስቲ ይህን ጽሑፍ እያነበብን ''በጣም የበደሉንን ሰዎች" እናስባቸው ምንድነው የሚሰማችሁ? ያ ስሜት ይቅርታ የማድረግና ያለ ማድረጋችሁን ያሳያል፡፡ ይቅርታ ትልቅ የፈውስ መንገድ ነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ እንደ አገር፣ ቤተሰብ፣ ቤተክርስቲያን እና ማህበረሰብ ይቅርታ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። በደል ካለ ይቅርታ መጠየቅ እና ይቅርታ ማድረግ አለ።
አንድ ታሪክ አንብቤአለው ታሪኩ በ2ኛው የአለም ጦርነት ወቅት ቤተሰቦቹን በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉበት ብዙ መከራ ስላለፈ አንድ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ከብዙ አመታት በኃላ ቤተሰቦቹንና ብዙ ሰዎችን ጭምር እንዲገደሉ ያሰቃያቸው ሰው (ኮሌኔል ) ወደ ሌላ ሸሽቶ በችግር ሆኖ እዚህ ሰው እጅ ይወድቃል፡፡ የዚህ ሰው ውሳኔ ይደንቃል፡፡ ሰውየው ባያውቀውም ይህ ሰው ለዚያ የቤተሰቦቹ ገዳይ ቸርነት እንዳደረገለት ይተርካል መፅሐፉ፡፡ ድንቅ ነው፡፡ ለሰዎች ቸርነት ማድረግ ምንም መልካም ቢሆንም ታላቅ የሚያደርገን ግን ለበደሉን ቸርነት ስናደርግ ነው። ስንቶቻችን ነን የገፉን ሰዎች በእጃችን ሲወድቁ ግፍ የማናደርግ ወይም የማንበቀል?
የይቅርታ ውሳኔ ራስን ለሌሎች መስዕዋት ከማድረግ ጋር ይመሳሰላል፡፡ በድሎን መልሶ ይቅር ማለት ሁለት ጉዳት ይመስላል ግን ትክክለኛ ይቅርታ ማድረግ አስቀድሞ የተጎዳንበትን ማደስ ነው መሻር ነው። በሰዎች ተጎድለናል? መፍትሄው ይቅርታ አድርጎ መሻገር ነው።
ስማችንን ያጠፉ ሰዎችን፤ የከዱን ቤተሰቦቻችንን፤ ፍቅረኛዎቻችን፤ የትዳር አጋሮቻችን፤ የስራ ባልደረቦቻችንን እንዴት ይቅር ማለት ይቻላል? ይቻላል ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የማንችለው አያዘንምና። ብዙዎቻችን ይቅርታ የማናደርገው ራስ ወዳድ ስለሆንን ጭምር ነው።
ብዙ ሰዎች የተፈወሰ ህይወት የሌለን ይቅርታ ለማድረግ ውሳኔ ማድረግ ስለማንፈልግ ነው። ብዙ ጊዜ ይቅርታ የማያደርጉ ሰዎች በደልን ይቆጥራሉ ሰዎችን የበደሉትን አያስቡም፡፡ የተበደሉበትን ቀን፤ ሁኔታ ሳይቀር የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ አይነት ወገኖችን ሳስብ እንዴት ነው ይቅርታ የሚያደርጉት? " ፍቅር በደልኝ አይቆጥርም" 1ኛ ቆሮ 13:5
የሰውን በደል የሚቆጥሩ ሰዎች ከጌታ ዘንድ ይቅርታ ካለመቀበላቸውም ሌላ የእነርሱ በደል እንዳይሰረይላቸው ይሆናል፡፡ "እግዚአብሔር ይቅር እንድንለው የማይፈልገው በደል አለመኖሩ በራሱ አስገራሚ ነው።"
በማንበዳደልበት አለም ላይ አይደለም ያለነው በደል ሊኖር ይችላል፣ ለምን የማንበድል የማንበዳደል ፍጹማን ሰዎች አይደለንም፡፡ መበዳደል ካለ ይቅርታ መጠየቅና፥ ማድረግ አለ፡፡
የበደሉትን ሰው ይቅርታ የማይጠይቁ ሰዎች ለበደላቸው ይቅርታ ማድረግ ይከብዳቸዋል፡፡
ዘማሪ ዶ/ር ደረጄ ከበደ፦
" ወንድሜን ማቁሰሌ እጅግ ይረሳኛል
የተበደልኩትን መቁጠር ይጥመኛል"
ይላል፡፡
ይቅርታ ማድረግን በቀላሉ እንለማመድ፡፡ ስለ ይቅርታ መጽሀፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎችን እንከተል፡፡ ይቅርታ ለማድረግም እንጸልይ። እግዚአብሔር የማንችለውን ትዕዛዝ አይሰጠንም፡፡ ይቅር ስንል ፥ ነገአችን ይፈወሳል፥ ህይወታችን ይለመልማል፡፡ በህይወታቸው ደስታ ከሌላቸው ሰዎች መሀል ይቅርታ የማያደርጉ ናቸው፡፡
ምን አታገለን፤ የሰዎችን በደል ታቅፈን የምንዞረው? ስለ ወንድሞቻችን ልናስብ የሚገባ ስንት ጥሩ ነገር እያለ ክፉ ለምን እናስባለን፡፡
"የማይበድል ማን ይሆን? የሌሎች ይቅርታ የማያስፈልገው?"
ይቅርታ ውሳኔ ነው ምርጫም ነው። አሁን መወሰን እንችላለን ይቅር ለማለት፡፡ ይቅርታ ውሳኔ ይፈልጋል፡፡ አዲስ ነገር የሚመጣው በአሮጌ እይታ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሚያውቀው የእኛ በደል አይበልጥምን? ይቅርታ ትምህርት ነው ይቅርታ ፈውስ ነው።
........ይቀጥላል....
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#የመሪ_ፍጻሜ_እንደ_አማካሪዎቹ_ነው!!
በዚህኛው ጽሑፍ መሪዎችንና አማሪዎችን እንመለከታለን። መሪ እንደ አማካሪዎቹ ነው። በሰዎች ህይወት ውስጥ ከምክር ጋር በተያያዘ ሶስት አይነት ነጥቦችን ማንሳት እንችላለን።
፨ምክርን አለመስማት
፨ የተሳሳተ ምክርን መከተልና
፨ምክርን መቀበል ናቸው።
ሰው በብዙ ነገር ውስን ነው ከዚያ የተነሳ ምክርና አማካሪዎች ያስፈልጉታል። መሪ ለመምራት የግድ ሽማግሌ መሆን አይጠበቅበትም የበሰሉ አማካሪዎች ካሉት ትክክለኛ አመራርን ሊመሰርት ይችላል። መንፈሳዊ መሪ ትክክለኛ ምክርን ከአራት ነገሮች ማግኘት ይችላል፦
፨ ከእግዚአብሔር ቃል / ከመጽሐፍ ቅዱስ
፨ ከመንፈስ ቅዱስ
፨ ከበሰሉ ሰዎች
፨ ከታሪክ / ከመጽሐፍት
ከእግዚአብሔር ቃል የጠለቀ መካሪ፤ ከመንፈስ ቅዱስ የላቀ አማካሪ የለም። በዚህ ውስጥ የበሰሉና የምክር መንፈስ ያለባቸው ሰዎች ያስፈልጉናል። እግዚአብሔር ልጆቹን በተለያየ መንገድ ይመክራል በቃሉ ይመክራል፤ በመንፈሱ ይመክራል፤ በሰዎች ውስጥ ሆኖ ይመክራል። ሁሌም ምክርን ለመስማት የተዘጋጀን እና ምክርን የምንለይ መሆን አለብን።
አብሶ መሪዎች የበሰሉ አማካሪዎች ሊኖሯቸው ያስፈልጋቸዋል። የቤተክርስቲያን መሪዎች፤ የአገር መሪዎች በተለያየ ስፈራ ያሉ መሪዎች የበሰሉ አማካሪዎች ሊኖሯቸው ይገባል። ህጻናት አማካሪዎች ያሉት መሪ ምንም ታላቅ ራዕይ ቢኖረው እርምጃው በምክሩ ልክ ነው። ቢሞግቱንም የበሰሉ መሪዎች መኖራቸው ለመንገዳችን ፍጻሜን ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ
“በመልካም ሥርዓት ሰልፍ ታደርጋለህ፤ ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው።”
— ምሳሌ 24፥6
በዙሪያችን የሰበሰብናቸው የእኛን ሐሳብ የሚደግሙ ደጋፊዎች (ቲፎዞዎች) ማከማቸት እርምጃችንን አጭር ያደርገዋል። ለምን? እንዴት የሚሉና ለእኛ ቢመችም ባይመችም የተሻለና ዘላቂ ትክክለኛ አኪያሄድን የሚያሳዩ አማካሪዎች ያስፈልገናል። ሁሉም የምክር ጸጋ የለውም። አገልጋይ ሁሉ መካሪ መሆን አይችልም። ይህ አገልግሎት የተሰጣቸው እንዲሁም በህይወት ተሞክሮ ቀድመው መምከር የሚችል ስብዕና ጋር የደረሱ ሊመክሩ ይችላሉ። አንዳንድ አገልጋዮች በጸጋ ታላቅ አገልግሎት ይሰጡና ምከሩ ሲባሉ ሲኦል የማይመክረውን ምክር ይመክራል። ምክር ለተሰጠው ነው።
..ይቀጥላል.....
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
የቴሌግራም ቻናሌን ይቀላቀሉ
#ለውጥ_ራስን_ከመለወጥ_ይጀምራል!!
"አንተ ልታየው የምትፈልገውን ለውጥ ራስህ ሁነው።" ማህተመ ጋንዲ
ለውጥ ለሚፈጥራት እንጂ ቁጭ ብሎ ለሚጠብቃት አትገኝም። እንደ አገር፣ እንደ ማህበረሰብ፣ እንደ ቤተክርስቲያን፣ እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ግል የምንፈልጋቸው ለውጦች ያለ እኛ ተሳትፎ አይመጡም።
አስተያየት በመስጠት እና በየ ሚዲያውና በየቦታው የተሰማንን በመናገር 'ብቻ' ወይም ደግሞ በግል ህይወታችን ላይ በምኞት ብቻ የሚመጣ ለውጥ የለም። ለውጥ የሚጀምረው ራስህን በመለወጥ ነው። ለራሳችን ባልሆንበት ለሌሎች መትረፍ አይቻልም። ስለዚህ ለለውጥ ማሰብ፣ መነሳት፣ መስራት ውጤት እስኪመጣ መትጋት ይፈልጋል።
ለለውጥ የማይሰሩና ከሌሎች ለውጥን የሚጠብቁ ሰዎች ሁልጊዜም ለውጥን በሁሉ ነገር ከሰዎች የሚጠብቁ ግን ደግሞ ለመለወጥ እና ለመለወጥ ምንም ተነሳሽነት የሌላቸው ናቸው። ለውጥ የሚጀምረው ራስን ከመለወጥ እና ለመለወጥ ከመነሳት ነው። ራስህ መለወጥ ሌሎችን ለመለወጥ ሁሉ ምክንያት ይሆናል። ሌሎች እንዲፈጥሩት የምትጠብቀውን ለውጥ አንተ ፍጠረው። ለለውጥ በሆነ ትግል ማለፍ ለውጥን ለማምጣት በር ነው። ለውጥ የሚመጣው በህልም ወይም ቁጭ ተብሎ አይደለም እንዲመጣ በምንፈልገው ነገር ለውጥ በማምጣት በመነሳት ነው።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#አምስቱ_ቁጭቶች!!
በህክምና ሙያ ውስጥ አመታትን ያሳለፈችው ቦኒ ዌር (Bonny Ware) እንዲህ ትላለች፦
ለብዙ አመታት የሞትን ጽዋ ለመጎንጨት የመጨረሻዋን ህቅታን የሚጠባበቁ በሽተኞች ጋር እሰራ ነበር። የህይወታቸውን የመጨረሻ ከሶስት እስከ አስራ ሁለት ያህል ሳምንታት አብሬያቸው እቆያለሁ። ስለ ጸጸታቸው አሊያም ባልሰራሁት ወይም በሰራሁት ኖሮ ስለሚሉት ጉዳይ ሲናገሩ ታዲያ ተመሳሳይ ጭብጦች ከብዙ አንደበቶች ይፈልቃሉ። በጣም ሲደጋገሙ ያስተዋልኳቸው አምስት ናቸው።
አንድ፦ ህይወቴን ሌሎች ሰዎች እንደሚጠብቋት ሳይሆን ለራሴ ሐቀኛ ሆኜ ኖሬያት ቢሆን ኖሮ
ሁለት፦ ያንን ያህል ከመጠን ባለፈ ስራ ተወጣጥሬ ባልኖርኩ ኖሮ
ሶስት፦ ስሜቶቼን የመግለጽ ድፍረት ቢኖረኝ ኖሮ
አራት፦ ከጓደኞቼ (ከቤተሰቦቼ) ጋር ብዙ ጊዜ በተገናኘሁ ኖሮ
አምስት፦ ለራሴ ደስተኝነትን ፈቅጄለት ቢሆን ኖሮ
(የስሜት ነጻነት - ፓውሎ ኮሆልዮ ገጽ 113-114)
ጸጸት በተለያዩ መንገዶች በሰው ህይወት ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ። ከላይ የተጠቀሱት ሐሳቦች ቀላል ይመስሉ እንጂ በህይወታቸው ሰዎች ባለመድረጋቸው የተጸጸቱባቸው ነገሮች ናቸው። ብዙ ሰዎች ደስታን ለነገ እያለ ዛሬያቸውን ለውጥረት ሸጠዋል፣ ገንዘብ ስራ እያሉ ለቤተሰብንና ለጓደኞችን ጊዜን መስጠት ትተው ለሌላ ነገር ጊዜያቸው ተሽጧል፣ ስሜታቸውን ሳይናገሩ በይሉኝታ ኖረዋል መሆን ያለባቸውን ሳይሆን መሆን የሌለባቸውን አስመስለው ራሳቸውን ገለው አልፈዋል፣ አንዳንዶች ደግሞ መሆን ያለባቸውን ሳይሆን ሰዎች የሚጠቁባቸው ኖረው አልፈዋል።
በወጣትነታቸው ጌታን የማገልገል ዕድል ኖሯቸው ዛሬ ነገ እያሉ ዕድሜያቸው የተበላ፤ ቤተሰቦቻቸውን መርዳት በሚችሉበት ሰአት ሳይረዱ ቤተሰቦቻቸው ያለፉ፣ መሆን የተገባቸውን ባለመሆን ምክንያት በቁጭት ያለፉ ብዙዎች ናቸው። ዛሬም እኛም ይህን ጽሑፍ ስናነብ ራሳችን ማየት ይሁንልን። ራሳችንን አንይ።
/channel/theideaofs
ሰዎች ስለ አንተ ገምተውና አስበው "እንዲህ ነው" ብለው በልካቸው ሊሰፉህና የሰፉልህን ሊያለብሱህ ሲፈልጉ አትገኝ፣ ልካቸውን ሳይሆን ልክህን ኑር። ሁልጊዜም አንተ አምነህና ሆነህ በተገኘህበት መንገድ እንጂ ሰዎች ስለ አንተ ገምተው በፈጠሩት መንገድ ላይ አትገኝ።
/channel/theideaofs
#ሐዋሪያው_ዳንኤል_መኮንን #የፈውስ_ሐዋሪያ
#ዘሪሁን_ግርማ
በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ቀደምት አባቶች መሐልና ጉልህ ስፍራ ካላቸው የእግዚአብሔር ሰዎች መሐል አንዱ ሐዋሪያው ዳንኤል መኮንን ናቸው። በኦሎንፒያ መሰረተ ክርስቶስ ታላቅ ሪቫይቫል ሲነሳ እግዚአብሔር እግዚአብሔር በታላቅ እጅ የተጠቀመባቸው ናቸው። በአገራችን ከመጋቢ አሰፋ አለሙ በመቀጠል በታላቅ የፈውስ አገልግሎት የተነሱ ሰው ናቸው።
በ1950ዎቹ አጋማሽ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያናት ከወንጌላውያኑ (ቀደምት በሚሽነሪ ከተተከሉ) ቤተክርስቲያናት ወጣቶች ወደ መንፈስ ቅዱስ ሙላት ( Pentecostal ) እየገቡ የነበረበትና ብዙዎች በልሳን መናገርና የፀጋ ስጦታዎች መገለጥ የጀመሩበት ጊዜ ነበር። የዚያን ዘመን ሪቫይቫል ውጤት ከሆኑት መሐል ሐዋሪያው ዳንኤል መኮንን ይገኛሉ።
ዳንኤል መኮንን የተወለዱት በ1942 በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ቤተሰባቸው ሙሉ ለሙሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የነበሩ ሲሆኑ ሐዋሪያው ዳንኤልም የቤቱ የመጨረሻ ልጅ ነበር። ቤተሰቦቹ ምንም ዳግም የተወለዱ አማኞች የነበሩ ባይሆኑም ሐዋሪያው ዳንኤል ግን ከልጅነቱ ጀምሮ መንፈሳዊ ዝንባሌ እንደነበራቸው ይነገራል። ብዙ በሽታዎች በህይወታቸው በማለፋቸው ከሞት መካከል ወተዋል።
ዳንኤል በ16 አመቱ የሐዋርያት ስራ መፅሐፍን አነበበ። በሐዋሪያቱ እየሰራ በነበረው የተአምራትና የድንቅ አገልግሎት ይገረም ነበር። የሐዋሪያው ዳንኤልን የውስጥ መሻት ያውቅ የነበረ አንድ ጓደኛው ቀድሞ በሐዋርያት ዘመን ይሰራ እንደ ነበረ ፀጋ የሚገለጥባቸው ሰዎች አሉ ብሎ ወደ አንድ ጉባኤ ጋበዘው። ቦታው አለም ማያ ሆቴል ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ የሙሉ ወንጌል ፀሎት ቤት ነበረ። ቀኑ ግንቦት 19, 1959 ነበረ። ዳንኤል መኮንን ለጌታ ራሱኔ አሳልፈው የሰጠውና ለክርስቶስ ህይወቱን የተማረው በዚያን ቀን ነበር።
ወጣቱ ወዲያው አገልግሎት ጀመረ። የሰፈሩ ወጣቶች ሰብስቦ የአዳር ፕሮግራም ማድረግና በተረዳው ወንጌልን መመስከር ጀመረ። አንድ ቅዳሜ ከሰአት በኃላ ከጓደኛው ጋር እየተጨዋወቱ ሲሔዱ " በአዲስ ቋንቋ" ታውቃለህ ብሎ ጠየቀው እንደማያውቅ ነገረው። በዚህ መንፈስ ቅዱስ መሞላት እንዳለ ጓደኛው ነገረው። ከዚያ ዳንኤል እንዴት ብዬ ልጠይቅ ሲለው። " በአዲስ ቋንቋ አናግረኝ" ብለህ ጌታን ጠይቀው አለው።
ዳንኤልም ወደ ቤቱ ከገባ በኀላ ልክ ጓደኛው እንዳለው። "በልሳን አናግረኝ " ብሎ ከመፀለዩ አንድ ራዕይ አየ። ራዕዩም 'የብርሃን ኳስ ጣሪያውን ቀዶ ሲወርድ ታየው። ወደ እርሱ ሲቀርብ እጅግ የሚያምር የሰው ቅርፅ ያለው ሆነ። ይህ በብርሃን የተጥለቀለቀ ሰው ወደ ታች እያየው ሰማያዊ ሐይል ህይወቱን አጥለቀለቀው። ጠዋት ነቅቶ ተንበርክኮ ሲፀልይ በአዲስ ቋንቋ መናገር ጀመረ። የዳንኤል ህይወትና አገልግሎት ተቀየረ።
#ታላቅ የእግዚአብሔር እጅ
ወጣቱ ዳንኤል መኮንን የመንፈስ ቅዱሰ ሙላትና የአዲስ ቋንቋ መናገር ከጀመረ በኃላ መንፈሳዊ አቅጣጫው ተቀየረ።
በዚሁ አመት በ1960 በኮሌጅ ተማሪነቱ ለኪስ ከሚሰጠው 50 ብር ላይ ከዘላለም ተፈራ 15 ብር እየከፈለ በመስፍን ሐረር መንገድ ቤት በመከራየት " ተአምረ ኢየሱስ ፀሎት ቤት" በማለት መፀለይ ጀመሩ። በዚያ ጊዜ የቻፕሉ መሪ ሆኖ ተመረጠ።
ዳንኤል ጌታን ከማግኘቱ በፊት በውስጡ ይንቀሳቀስ ሐሳብ በ1961 ላይ በሐይል በውስጡ ይመላለስ ነበር። የሐዋርያት ስራ መፅሀፍ ላይ ያለው የእግዚአብሔር ስራ። ከዚያም ዳንኤል ሰው በምድሪቱ ላይ ሰው እንዲያስነሳ ይፀልይ ነበር።
" እባክህ ለምድሪቱ የተረፈ ላንተ የመሆን በትር አስነሳ" እያለ ይፀልይ ነበር።
በሳምንቱ ጋሽ አሰፋ አለሙ (አሁን ፓ/ር ዶ/ር)
"በእግዚአብሔር የተላከ ሰው" የሚል መፅሀፍ ይሰጠዋል። መፅሀፍ ውስጥ ያለው ሐሳብ ያንን ሰው እግዚአብሔር እንዴት ለአገልግሎት እንደጠራው የሚተርክ ነበር። ይህ ለዳንኤል ትልቅ ጥቆማ ነበር።
መፅሐፉን ካነበበ በኃላ በእግዚአብሔር ፊት በመደፋት " ሬሴን ለአንተ መስጠት እፈልጋለሁ ግን አላውቅበትም" ብሎ ለጌታ ተናገረ። ጌታም በማይረሳ ድምፅ " እራስህን እንዴት እድርገህ እንደምትሰጥ አስተምርሃለው" አለው። ያን ቀን ህይወቱ በጌታ መንፈስ ተጥለቀለቀ።
ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች ስለ ሐዋሪያው ዳንኤል መኮንን ሲናገሩ የሚስማሙበት
"በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሰው እንደሆነ ነው"። አገልግሎታቸው አየሰፋና እየጨመረ መጣ። ሰዎች ነፃ ይወጡና ይፈወሱ ነበር። ፅዮን የሚባል የዝማሬ አገልግሎት ጀመሩ በዚያም እያገለገሉ ሌላ ችግር ተከሰተ በፊት ከነበሩበት ቦታ ተሰደዱና ሰሜን ሆቴል አካባቢ ሌላ ቤት ተከራዩ። በዚያም ብዙም አልቆዩም ተሰደዱና ጫካ ገብተው ማምለክ ጀመሩ። ይህ የሆነው በ1963 አመተ ምህረት ነው።
በዚያ ወቅት እግዚአብሔር ለዳንኤል መኮንን ወደ "መሰረተ ክርስቶስ" ቤተክርስቲያን እንዲሄዱ ተናገረው። በኦሎንፒያ 500 ሜትር ገባ ብሎ ነው። ያ ቦታ በ1953 አመተ ምህረት የተመረሰተው የሜኖናይት ቤተክርስቲያን ቦታ ላይ ነው መሰረተ ክርስቶስ አገልግሎትዋን የጀመረችው። እነ ዳንኤል መኮንን የገቡት እዚያ መሰረተ ክርስቶስ ቤተክስቲያን ነው። ዳንኤል በ1965 ሙሉ ለሙሉ ራሱን ለጌታ አሳልፎ በመስጠት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ።
የፀጋ መገለጥ
ሐዋሪያው ዳንኤል መኮንን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ወደ ሐዋሳ ይሄዳል። ያኔ ገና ትምህርቱን በጨረሰ ማግስት ነበር። እግዚአብሔር በህይወቱ የፀጋ መግለጥን በላዩ ላይ በሐይል የጀመረው በሐዋሳ እንደሆነ ይስማማሉ። የአዋሳ ህይወት ብርሃን ቤተክስቲያን ለወጣቱ ዳንኤል በኮንፍራንስ ላይ እንዲያገለግል ጋበዙት። ሁሉም አጋጣሚ ይመስላል እግዚአብሔር ግን እየጀመረ ነበር። በተዘጋጀው ኮንፍራንስ ላይ ሲያገለግል ብዙ በሽተኞች ተፈወሱ እውራኖች በሩ የማይሰሙ ሰሙ በዚያ ጊዜ በከተማው የታወቀ እውር ለማኝ በዳንኤል አገልግሎት ተፈወሰ። ብዙ ድንቅ ሆነ።
#የፈውስ ሐዋሪያ
ዳንኤል መኮንን ከአዋሳው አገልግሎት በኃላ ወደ ጅማ ከአሰፋ አለሙ ( መጋቢ ዶ/ር) ጋር በመሄድ አሰፋ አለሙ ስር በመሆን እያገለገለ እግዚአብሔር ለሚቀጥለው ስራ እንዲዘጋጅ ረዳው። ከአሰፋ አለሙ ጋር አንድ አመት ያህል አገለገለ።
አሰፋ አለሙ ቀደም ባሉት ጊዜያት የመንፈስ ሙላት በሐረር ካገኛቸው የመጀመሪያዎች አንዱ ነው። ይህ ሰው አስተማሪ፤ የጥበብና የእውቀት መንፈስ የነበረው ሲሆን መንፈስን የመለየት ፀጋም ነበረው። ጋሽ አሰፋ አለሙ ድንቅ የእግዚአብሔር ሰውና በዚያ ትውልድ መካከል የተቀባና ዘመኑን ቀድሞ የሄደ ሰው ነው። ዳንኤል መኮንን ለአንድ አመት እዚህ ሰው ስር ሆኖ ተምሯል አገልግሏልም።
ሐዋሪያው ዳንኤል መኮንን " የአባትነት ልብ ያለው ሰው ነበር። አሁንም ድረስ ነው" ይላሉ። በዳንኤል መኮንን አገልግሎት ትልቅ ተፅእኖ ከፈጠሩ ሰው መሐልና የመጀመሪያው አሰፋ አለሙ ነው። በዚያ ውስጥ ግን እግዚአብሔር ዳንኤልን ለሚቀጥለው ስራ እያዘጀውና እያሰደገው ነበር።
.....ይቀጥላል...
#እነማንን_ታውቃለህ_ሳይሆን_ምን_ታውቃለህ?
"ከማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ" ብቻ ሳይሆን ምን እንደምታስብ፤ ምን እንደምታስተምር፣ ለምን እንደምታስብ ሳውቅ ማንነትህን እነግርሃለሁ። መባል አለበት። አብሮ መዋል በሰዎች ህይወት ላይ (መልካምም ክፉም) ተጽጽኖ ያመጣል። ያ ማለት ውሎ ብቻ አመለካከትህን ይቀይረዋል ማለት አይደለም።
ረጅሙና ዘላቂው ትምህርትህ፤ ህይወትህ እና አኪያሄድህ ላይ መስራት ነው። በሰዎች ላይ የተመሰረተ ከፍታ ዘላቂ አይደለም እርግጥ ነው ከሰዎች አንማራለን። ምን እየተማርን አጥርተን እንወቅ እንጂ ከሰዎች ሁሌም እንማራለን። ዋናው የቦታ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአኪያሄድና በእውነት ላይ የተመሰረተ ይሁን።
ከሰዎች ጋር ስትውል ከእነርሱ መማር ያለብህን ተካፈል። ህይወትህን ግን በሰዎች ላይ አትመስርት። ሁሉም ሰው የሚያውቀው ከእውቀት ከፍሎ ነው። ሰዎች ላይ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል ላይ መመስረት ያዘልቃል። ዘመኑ የጎራ እንደ መሆኑ ልክ እንደ "ብሔር ፖለቲካ" ሁሉ በተከፋፈለ እና በራሳቸው ከወንጌል አላማ ከወጣ አኪያሄድ መተባበርም የትም አያደርስም።
ነጥቡ ከማን ጋር ትውላለህ ሳይሆን አንተ ምን ላይ ቆመሃል? ነው፤ እነማንን ታውቃለህ ሳይሆን ክርስቶስንና የእግዚአብሔር ቃል ጠንቅቀህ ታውቃለህ ወይ? የሚለው ነው። ነገ ሰዎች አብረውህ ኖሩም አልኖሩም እውነት ላይ ቆመሃል ወይ? ራስ የሆነው ክርስቶስ እየተከተልክ ነው ወዮ? ጎራ መሰብሰብ በታዋቂ ሰዎችም መታጀብ የትም አያደርስም። የህይወት ዘመንህ መመስረት ያለበት በእግዚአብሔር ቃል እና በክርስቶስ ላይ ብቻ ነው።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs
#ኦርተዶክሳዊ_ተሃድሶ #ከታሪክ_እንማር!!
ካቶሊክ ከ 13ኛ እስከ 18ኛው ምዕተ አመት ትሰራበት የነበረው "ኢንኪውዜሽን የተሰነ "የሐይማኖት ፍርድ ቤት" ነበራት። ቤተክርስቲያኒቱ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው የተገኙ (ከላቲን ቩልጌት) ውጪ ወይም መጽሐፍ ቅዱሰን ከላቲን ወደ እንግሊዝኛ የተረጎሙ ሰዎችን እስከ ነፍሳቸው በእሳት ታቃጥል ነበር። ዊልያም ቴንደልን የሞተው በዚህ መልክ ነው። ከሞቱ በኃላ እንኳ ከተቀበሩበት ወተው ራሳቸው በእሳት እንዲቃጠሉ የተደረጉ እንደ ጆን ዊክሊፍ ያሉ አባቶች ነበሩ። ቤተክርስቲያኒቱ ከመንግስት ጋር የስልጣን ሲሶ ስለነበራት ብዙዎች ገድላለች አሳዳለች። እንደዚህ አይነት ስህተት በታሪክ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ተከስተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎችና እውነተኛ የታሪክና የቤተ-ክህነት መምህራን ነበሯት። በአጼ ዘርያዕቆብ ዘመን ንግስና በቤተክርስቲያኒቱ እውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስን ትህምርት ያስተምሩ የነበሩ ደቂቀ እስጢፋኖስ ወንጌልን በማመናቸው በአጼ ዘርዓያዕቆብ ተገድለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር ቃል ትምህርት መመለስ እና አሰራርዋን መመልከት ያለበት ጊዜው አሁን ይመስለኛል።
የቀደመውን ስህተት መድገም ሳይሆን ካለፈው ስህተት መማር ያስፈልጋል። ቤተክርስቲያኒቱ መታደስ እንዳለባት አንስተው ከሞገቱ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ምሁራን መካከል ነጋድረስ ገብረህይወት ባይከዳኝ፣ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ዘብሔረ አድዋ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ እንደሚገኙበት ጸሐፊ ጸጋአብ በቀለ "ተሐድሶ" በተሰኘው መጽሐፉ ላይ በገጽ 141 ላይ ይናገራል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ማሳደድዋ በነደቀቂ እስጢፋኖስ ላይ ያቆመ አልነበረም ጉምቱ የሆኑት የኢትዮጵያ ምሁር አለቃ ታዬ "የኑፋቄ ትምህርት ሰራተኞች" በማለት እንዳወገዘቻቸው
ጸጋአብ በበቀለ በ "ተሃድሶ" ገጽ 139 ላይ ይናገራል። አንድ ታሪክ አንብቢያለሁ።
በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ
"የግብፅ ጳጳሳትን የበላይነትና በቤተ መቅደስ የተሰራፋዉን ኢ-መፅሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በመቆም በግልፅ የሞገቱና ለእውነት ራሳቸውን የሰጡ ታላቅ ሰው ነበሩ፦
አለቃ ታዬ የተቃውሞ ትምህርት ያስተምራሉ በሚል በጳጳሱ ፊት ቀረቡ ። ስለተከሰሱበት ነገር ራሳቸውን መከላከል ሲጀምሩ ጳጳሱ በቁጣ አቋረጣቸውና አንተ አህያ ኃይማኖትህ ምንድነው? ሲሉ ዘለፏቸው። እርሳቸውም በኢትዮጲያ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የተሾሙትን ግብፃዊ ጳጳስ በክርስቲያናዊ እምነታቸው ላይ እንዲቀልዱ ባለመፍቀድ፦
በእርግጥ እኛን የማይረቡ አህዮች ያሰኘን እኮ በቤተ-ክርስቲያናችን ላይ እንደ እርስዎ ያሉትን ባዕዳን መሸከማችን ነው በማለት ጳጳሱን አሸማቀቁ።"
አለቃ ታዬ ገብረ ማርያም(1853-1916)
አለቃ ታዬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ካፈራቻቸው ለአገሪቱ ታላቅ ውለታ ከዋሉ ጥቂት ምሁራን አንዱ ናቸው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤክርስቲያን ትምህርቷን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመለስና የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን በማስተማር ትውልዷን ማስታጠቅ አለባት። በዚህ ዘመን ያሉት የቤተክርስቲያኒቱ ወጣቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተፋኑ መሆናቸው የታወቀ ነው። ቀደምቷ መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ እንዲተረጎም ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ የመመለስ ተሃድሶአዊ ዘመቻ ውስጥ ልትገባ ያስፈልጋል።
እውነት አንድ እርሱ መጽሐፍ ቅዱስ፣ እምነት አንድ ነው በክርስቶስ የመስቀል ስራ በትንሳኤው ማመን፣ በክርስቶስ በማመን በሚገኝ ድነት ማመን፣ ክርስቶስን የሸፈነውን ሰዋዊ ትህምርቶችን አንስቶ ክርሰቶስ ተኮር የሆነውን ወንጌል ብቻ መስበክ። ያኔ ቤተክርስቲያኒቱ ትታደሳለች። ቤተክርስቲያኒቱ ወደ ወንጌሉ ከተመለሰችና በአውደ ምህረቶቹ ላይ ወንጌሉ ከተሰበከ እውነት ለመናገር ማንም እምነቱን ትቶ ወደ ሌላ እምነት አይሄድም። መሄድም አይጠበቅበትም።
ተሃድሶ የማያስፈልገው ቤተክርስቲያን የለም። የወንጌላውያን ቤተ-እምነትቶችም ተሃድሶ ያስፈጋቸዋል። ተሃድሶ የማያስፈልገው ተቋም ወይም ግለሰብ የለም። ለዚህም ነው ወደ እግዚአብሔር ቃልና ወደ ወንጌሉ መመለስ ያለብን።
ዘሪሁን ግርማ
/channel/theideaofs