1583422
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው። መረጃ እና መልዕክት ፦ 0998999899 ማርኬቲንግ ፦ 0979222111 ወይም 0979333111 @tikvahuniversity @tikvahethAfaanOromoo @tikvahethmagazine @tikvahethsport @tikvahethiopiatigrigna #ኢትዮጵያ
" መጀመሪያ በካሬ 35 ሺሕ ብር የነበረውን ክፍያ አሁን 'በካሬ 82 ሺሕ ብር ሆኗል' በሚል ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አደረጉብን " - ለቤት የተደራጁ መምህራን
መምህራን በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከዚህ ቀደም በተጀመረው አሰራር መሰረት በካሬ 35 ሺሕ የነበረው ክፍያ አሁን " በካሬ 82 ሺሕ ብር ተደርጎ፣ 25% የቅድሚያ ክፍያው ከፍተኛ ጭማሪ ተደርጎበታል " ሲሉ መምህራን በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ቅሬታ አቅርበዋል።
መምህራን የቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማህበራቸው በኩል በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ይስተዋላሉ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም መምህራንን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞችን የቤት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ከንግድ ባንክ ጋር ከዚህ ቀደም መፈራረሙ ይታወሳል።
በወቅቱ እንደተገለጸው፣ ስምምነቱ በአነስተኛ የወለድ መጠን በ25/75 የብድር መርሃግብር የሚከናወን ሲሆን፣ 25 በመቶ የመንግስት ሠራተኛው ቆጥቦ፣ 75 በመቶ የባንክ ብድር የሚቀርብለት፣ ብድሩን በ20 ዓመታት የሚከፈልበት ነው።
መምህራኑ በወቅቱ በስምምነቱ ጥሩ ቢሆንም " 25 በመቶ የመቆጠብ አቅም የለንም " ብለው የነበረ ሲሆን፣ የከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሰጡት ምላሽ፣ " መቆጥብ ለማይችሉት የኪራይ ቤት ገንብቶ ለመስጠት እየተሰራ ነው " ሲሉ ገልጸው ነበር።
መምህራኑ አሁንስ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አሉ ?
" መምህራንን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ያደርጋል በሚል በወጣው መመሪያ መሰረት እያንዳንዳቸው 110 አባላት የያዙ 60 ማህበራት በከተማዋ ተደራጅተዋል።
ቦታው ተለይቶ ከተሰጠን ወዲህ አንዳንድ ኮንትራክተሮች የተወሰነ ግንባታ ጀምረው ነበር፤ የተወሰኑት አልጀመሩም። ግን መጀመሪያ በካሬ 35 ሺሕ ብር የነበረው ክፍያ አሁን በካሬ 82 ሺሕ ብር ሆኗል በሚል ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አደረጉብን።
በወቅቱ የነበረው በካሬ 35 ሺሕ ብር ነበር። ከከፈልን በኋላ ሲጓተት ቆይቶ ከወር በፊት ግንባታውን ጀመሩ። ግን በኋላ ASTU ጥናት አጥንቶ በካሬ 82% ደርሷል ተባለ። በዚህም ለምሳሌ 3 ሚሊዮን የነበረ ውል ወደ 9 ሚሊዮን ሆኗል።
ጉዳዩን የሚያውቀውን የአዲስ አበባ መምህራን ማህበርን ስንጠይቅ 'እኛ ሳናውቅ እንዴት እንዲህ አይነት ነገር ይሆናል ?' የሚል ምላሽ ነው የሰጡን። ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀናል።
ቤቱ ይጠቅመናል ብለን 25% የቅድሚያ ክፍያ ገንዘብ የከፈልነው ከሁለት፣ ሦስት ማይክሮፋይናንስ ተበድረን ነው። የጋራ መኖሪያ ቤት እድል ተጠቃሚ ከሆኑት ወደ 660 መምህራን አብዛኛዎቹ ተበድረው ነው የከፈሉት።
በዛ ላይ ባንክ ያመቻቸልን 75 በመቶ ብድር በምን ውል እንደሚከፈል አልታወቀም። 14% ነው የተባለው ኢንተረስቱ። ጫማ፣ ልብስ መቀየር የከበደን ሰዎች ነን። አብዛኞቻችን ችግር ላይ ወድቀናል " ብለዋል።
25 ፐርሰንቱን 400 ሺሕ፣ 500፣ 700 ሺሕ እንደየካሬው ብዛት ቅድሚያ ከፍለው ካጠናቀቁ በኋላ ግንባታ ሊጀመር ሲል " የግንባታ እቃ የዋጋ ለውጥ አለ " በሚል የተጨመረባቸው ገንዘብ ከሁለት እጥፍ በላይ መሆኑን ገልጸው፣ ለመክፈል አቅማቸው ስለማይፈቅድ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ለመምህራኑ ቅሬታ ምላሽ የጠየቀው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ መምህራን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለዘመናት ሲጠይቅ መቆየቱን አስታውሶ፣ ስለክፍያ ጭማሪ ግን ጉዳዩን የያዘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ማብራሪያ እንዲሰጥ መርቷል።
የአ/አ ከተማ መምህራን ማህበር ምን መለሰ ?
የከተማዋ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ድንቃለም ቶለሳ የስልክም ሆነ የፅሑፍ መልዕክት ባይመልሱም፣ ቅሬታ አቅራቢ መምህራኑ የማህበሩ ም/ፕሬዝዳንት ናቸው ያሏቸው፣ እሳቸው ደግሞ "የማህበሩ አመራር ነኝ" ያሉት አቶ አናንያ ደርሶ ግን የመምህራኑን ቅሬታ ይዘን ላቀረብነው ጥያቄ የተሰወነ ማብራሪያ ሰጥተውናል።
በሚያውቁት መረጃ መሰረት፣ " ASTU (የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ) ባደረገው ጥናት መሰረት አጠቃላይ የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታን በአማካሪነት ይዞታል፤ ካለው ወቅታዊ የዋጋ ንረት አኳያ የተወሰኑ ማሻሻያዎች አድርጓል " ብለዋል።
" ባለኝ መረጃ፥ ከመምህራኑ ለኛ ተፅፎ በዚህ ተጨምሯል፤ በዚህ ልክ ሆኗል የሚል የደረሰን ነገር የለም። ይደውላሉ እንጅ በደብዳቤ የመጣ ነገር የለም " ሲሉም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ነገር ግን መምህራኑ በከፈቱት የዋትሳፕ ግሩፕ "ከፍተኛ ጩኸት/ቅሬታ" እንዳለ ገልጸዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሌሎች የሚመለከታቸውን ተቋማትን ለማናገር ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
@tikvahethiopia
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ትግራይ ክልል፣ መቐለ ይገኛሉ።
ዛሬ ጥዋት ላይ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የህወሓት አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አንድ ቀን በመቐለ የሚያሳልፉት አምባሳደሩ ቀጠናዊ የፀጥታ እና ሰላም ፣ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ ቀደም ሀገራቸው አሜሪካ በህወሓት አመራሮች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏ የሚዘነጋ አይደለም።
ሃምሌ 8 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
#EthiopianAirlines
" አጠቃላይ የወጣው ወጪ 1.4 ቢሊዮን ብር ነው " - አቶ መስፍን ጣሰው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው የንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ ሲመረቅ ባደረጉት ንግግር፣ የአየር መንገዱ የደብረ ማርቆስ ከተማ የበረራ አገልግሎት ታሪክ ከ50 ዓመታት በፊት የጀመረ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ አየር መንገዱ "ዳሽ-6" (Dash-6) የተባሉትን አውሮፕላኖች ከአገልግሎት ውጪ ሲያደርግ፣ በረራው ላለፉት 20 ዓመታት በላይ ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል።
ለበረራው መቋረጥ ዋናው ምክንያት አየር መንገዱ ለሀገር ውስጥ በረራዎች የመደባቸው አውሮፕላኖች ትላልቅ በመሆናቸውና በጊዜው የነበረው ማኮብኮቢያ እነዚህን አውሮፕላኖች ማሳረፍ ባለመቻሉ እንደነበር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።
በዚህም የተነሳ የአካባቢው ማኅበረሰብ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ አድካሚ የሆነውን የአባይ ወንዝ ሸለቆ በማቋረጥ፣ 300 ኪሎ ሜትር በመኪና መጓዝ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
አቶ መስፍን ለአካባቢው ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ " ዛሬ አዲስ አበባ ወይም ባሕር ዳር ከ1 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ ደኅንነቱና ምቾቱ በተጠበቀ የአየር ትራንስፖርት መጓዝ ችላችኋል ፤ የዘመናት ጥያቄያችሁም መልስ አግኝቷል " ብለዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ጣቢያው የሙከራ በረራ ሲጀመር በሳምንት 3 በረራዎች ብቻ ይበቃል የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት ግን ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ በቀን 3 እና በሳምንት 21 በረራዎች መድረሱን ይፋ አድርገዋል።
ይህ እውነታ በአካባቢው ምን ያህል የታፈነ የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት እንደነበር የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቱን ዝርዝር መረጃ በተመለከተም፣ አውሮፕላን ማረፊያው 2,400 ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው በመሆኑ በመደበኛነት Q400 አውሮፕላኖችን፣ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ቦይንግ 737 አውሮፕላኖችን ማሳረፍ እንደሚችል አስታውቀዋል።
ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ከ4 ዓመታት በላይ የወሰደ ሲሆን፣ አጠቃላይ የወጣው ወጪም 1.4 ቢሊዮን ብር መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው አገልግሎት መጀመሩ ኢንቨስተሮችና ቱሪስቶች ወደ አካባቢው እንዲመጡ በማስቻል ለአካባቢው የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ ባለፉት 8 የለውጥ ዓመታት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች 5ኛው፣ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ካሉት ደግሞ 25ኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ግንባታቸው እየተጠናቀቀ ያለ 2 የአውሮፕላን ማረፊያዎች ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ አብስረዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሃምሌ 5 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" እኛ ብንኖርም ባንኖርም መበቀላችን አይቀሬ ነው " - ሞሽታባ ኻሜኒ
👉 " [እኔ ከተገደልኩ] ኢራንን ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ ጥቃት ለአንድ ዓመት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ተሰጥቷል " - ትራምፕ
በአሜሪካና በኢራን መካከል የተደረገው ተኩስ አቁም ስምምነት የፈረሰ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ዛቻዎችን እየተለዋወጡ ይገኛሉ።
አሜሪካና እስራኤል በከፈቱት ጥቃት አባታቸው የተገደሉባቸው የኢራን መንፈሳዊ መሪ ሞሽታባ ኻሜኒ፣ የአባታቸውን ደም መበቀል "አይቀሬ" መሆኑን ገልጸዋል።
" ይህ በቀል የአገራችን ፈቃድ ነው። ያለምንም ጥርጥር መፈጸም አለበት " ያሉት የ54 ዓመቱ መንፈሳዊ መሪ ' ይህ ጉዳይ በእኔም ሆነ በሌሎች ባለሥልጣናት ህልውና ላይ የሚመሠረት አይደለም። እኛ ብንኖርም ባንኖርም ይህ ጉዳይ መፈጸሙ አይቀሬ ነው ብለዋል።
መንፈሳዊ መሪው በአባታቸው ስርዓተ ቀብር ላይ ያልተገኙ ሲሆን የአባታቸውን ደም መበቀል እንደማይቀር የገለጹ በፅሁፍ ባሰራጩት መልዕክት ነው።
በሌላ በኩል፥ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ " 1000 ሚሳይሎች ተቀባብለው በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ላይ ተደግነዋል " ሲሉ ዝተዋል።
ኢራን ልትገድላቸው እንደዛተች የገለጹት ትራምፕ ይህ ከሆነ፣ ኢራንን ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ ጥቃት ለአንድ ዓመት እንዲፈጸም ትዕዛዝ መሰጠቱን፣ የአሜሪካ ጦርም ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
መረጀው ዶቼ ቨለ ሬድዮ ኤኤፍፒን ዋቢ በማድረግ ነው ያስነበበው።
ሃምሌ 4 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
ላፍቶ ሆስፒታል አካባቢ ለሚካሄድ አስቸኳይ ግንባታ ሲባል ከጀሞ 1 ወደ ጀሞ 3 የሚወስደው መንገድ ለ15 ቀናት ዝግ እንደሚሆን ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የጎርፍ አደጋ ስጋትን አስቀድሞ ለመከላከል በላፍቶ ሆስፒታል አካባቢ አስቸኳይ የቦክስ ከልቨርት ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ሲባል ከነገ ሐምሌ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት ከጀሞ አንድ መብራት ወደ ጀሞ ሦስት አደባባይ የሚወስደው መንገድ ለትራፊክ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ዝግ እንደሚደረግ ገልጿል።
በመሆኑም፦
- ከጀሞ አንድ መብራት ወደ ጀሞ ሦስት አደባባይ የሚወስደውን መንገድ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች፤ በላፍቶ ሆስፒታል ጀርባ አድርገው ወደ ጀሞ ሦስት አደባባይ እንዲጓዙ፤
- ከጀሞ ሦስት አደባባይ ወደ ጀሞ አንድ ሚጓዙ አሽከርካሪዎች፣ በሀጫሉ ሁንዴሳ ጎዳና አድርገው በቫርኔሮ አደባባይ በኩል መጓዝ የሚችሉ መሆኑን ባለስልጣን መ/ቤቱ ጠቁሟል።
ሃምሌ 3 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
የቤት ኪራይ ጭማሪ
" የ11.5% ጭማሪ አነስተኛ ይመስላል፤ በዓለምአቀፍ ደረጃ ሲታይ ግን እጅግ ከፍተኛ ጭማሪ ነው የተደረገው " - የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት
👉 " ሞሎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሥር ያሉ ሱቆች ቀድመው የገዙ የሚያከራዩበት ዋጋ ለመስማት የሚዘገንን ነው! "
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ዛሬ ጠዋት ይፋ ያደረገው የ11.5% የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ " እጅግ ከፍተኛ " ፣ " አብዛኛው ተከራይ ከፍተኛ ጭማሪ ከተደረበትና ከተፈናቀለ በኋላ ይፋ የተደረገ " በመሆኑ የዘገዬ ውሳኔ መሆኑን የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ለቲክቫህ ኢትዮጵያን ገለጸ።
የድርጅቱ መስራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ቁምላቸው አበበ በሰጡን ቃል፣ " 11.5% የሚለው ጭማሪ ከኛ ሀገር የዋጋ ግሽበት አንፃር ተመጣጣኝ ቢሆንም ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲታይ ከፍተኛ ነው " ሲሉ ተናግረዋል።
" በሌሎች ሀገራት የቤት ኪራይ ጭማሪ የሚደረገው ቤቱን ለማስጠገን የሚያስፈልግ ወጭ ታሳቢ ተደርጎ ከነጠላ አሀዝ ያላለፈ ጭማሪ ነው " ያሉት አቶ ቁምላቸው፣ " የኛ 11.5% ጭማሪ አነስተኛ ይመስላል፤ በዓለምአቀፍ ደረጃ ሲታይ ግን እጅግ ከፍተኛ ጭማሪ ነው የተደረገው " ሲሉ ገልጸዋል።
" ለዛውም ለቤቶቹ ፦
- ጥገና ለማድረግ፣
- ቀለም ለመቀባት፣
- ቤት ውስጥ ያሉ ነገሮችን ለማስተካከል ጭምር ነው ? ጭማሪ የተደረገው የሚለው ሳይታሰብ ለዋጋ ግሽበት ብቻ የተደረገ ጭማሪ ነው " ብለውታል።
የከተማዋ ቤቶች ልማት አስተዳደር ደግሞ፣ ጭማሪው " በጥናት የተደገፈ ፣ የነዋሪውን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ፣ አከራዮች ወቅታዊውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ ፍትሐዊ ገቢ እንዲያገኙ " የሚያስችል ብሎታል።
የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት በሌላ በኩል፥ " የቢሮው ውሳኔ እንደ መነሻ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፣ ማስተካከያው ይፋ መደረግ የነበረበት በግንቦትና ሚያዚያ ወር ነበር፤ በጣም የዘገየ ነው " ብሏል።
" አብዛኛው ተከራይ ከኪራይ ከተፈናቀለ፣ ከፍተኛ የኪራይ ጭማሪ ከተደረገበት በኋላ ነው ውሳኔው ይፋ የተደረገው " ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።
ተከራዮች በበኩላቸው፣ የኪራይ ጭማሪው 11.5% ሆኖ ከመወሰኑ በፊት ፦
• " ቤቴን ላድስ ነው"
• " ቤተሰብ ሊገባበት ነው " በሚል ሰበብ የተጋነነ ጭማሪ እንደተደረገባቸው ቅሬታ እያቀረቡ ሲሆን፣ ቲክቫህ ኢትዮጵያም ለዚህ ምን አይነት መፍትሄ ያስፈልጋል ? ሲል ድርጅቱን ጠይቋል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቁምላቸው አበበ፣ " የዚህ መመሪያ አንዱ ፈታኝ ነገር አፈጻጸሙ እንዴት ይሆናል ? እግር በእግር ተከታትሎ ማን ያስፈጽመዋል ? " የሚለው መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በፊት ቤቱ ተከራይቶበት የነበረው ዋጋና አሁን ስንት እንደሚሆን ስለሚታወቅ የጭማሪው አፈጻጸም ስርዓታዊ እንዲሆን አሳስበዋል።
" ዛሬ ይፋ የሆነው ውሳኔ፣ እንዴት ይፈጸማል ? ማስፈጸሚያ ስልቱ ምንድን ነው ? የሚለው ግልጽ አይደለም " ብለው በጥናቱ ድርጅታቸው እንዳልተሳተፈ አመልክተዋል።
" እንዲህ አይነት ጥናቶች ሲደረጉ እንደ እኛ አይነት የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችን፣ ተከራዩን፣ አከራዩን በግልጽ ማወያየት ይገባል " ብለዋል።
ጉዳዩ በአከራዮችና ተከራዮች መካከል ጭቅጭቅ እንዳያስከትል አፈጻጸሙ ለወረዳ ብቻ ሳይተው የበላይ የመንግስት አካል መከታተል አለበት ባይ ናቸው።
ከ50 እስከ 100% ኪራይ ጭማሪ እንደተደረገ፣ በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ፦
° ባለአንድ መኝታ ቤት ከ9፣ 10 ሺሕ ተነስቶ እስከ 22 ሺሕ ብር እንደደረሰ፤
° 15፣ 16 ሺሕ ብር ሲከራይ የነበረው ባለሁለት መኝታ ቤት 28፣ 30 ሺሕ መከራየትና መጠራት እንደተጀመረ ከዚህ ቀደም ማሳወቃቸውንም አስታውሰዋል።
" አሁን የወጣው ውሳኔ ቀድሞ ባስቸኳይ ይፋ እንዲደረግ፣ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበን ነበር " ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ " ያን ካሳሰብን በኋላ ዛሬ ይፋ የሆነው ውሳኔ የዘገዬ ነው " ሲሉም ተችተዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በበኩሉ፣ " ዋጋ ጭማሪው እና የውል እድሳቱ መነሻ የሚሆነው ከዚህ ቀደም በነበረው ውል ላይ የተቀመጠው የኪራይ ዋጋ ብቻ ነው " ሲል አስታውቋል።
የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት በሌላ በኩል በሰጠን ገለጻ፣ በቤት ኪራይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የመንግስት አገልግሎቶች፣ የንግድ ዘርፎች ላይ እንዲሁ ተመሳሳይ የዋጋ ጣሪያ የትርፍ ህዳግ ሊወሰን ይገባል ሲል በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል አሳስቧል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ስለአጠቃላይ ችግሩና መፍትሄው አክለው ምን አሉ ?
" ለቤት ኪራይ መወደድ ትልቅ ጫና የፈጠረው በኮሪደር ልማቱ በርካታ ቤቶች ፈርሰው በቂ ተጨማሪ ቤት ባለመገንባቱ በቤት ኪራይ ላይ የመጣው ጫና ነው። ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት፤ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፤ የኑሮ ውድነት አለ።
መንግስት በተለይ ለደመወዝተኛው የዋጋ ግሽበቱን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ጭማሪ ሊያደርግ ይገባል። ላለው የዋጋ ግሽበት አንዱ ምክንያት የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው። እጥረቱ በዘላቂነት ሊቀረፍ የሚችለው በተለያዩ አማራጮች መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ነው።
ሌላው ፥ በቤት ኪራይ ከፍተኛ ጭማሪ የሚያደርገው ህገወጥም፣ ህጋዊም ደላላ ነው። ከቤት ባለቤት ደውሎ 'ይህን ያህል ላከራይልህ' በማለት። ዘላቂው መፍትሄ በአከራይና ተከራይ መካከል ያለውን ደላላ በማስወጣት አከራዩ እና ተከራዩ የሚገናኝበትን የቴክኖሎጂ መተግበሪያ መዘርጋት ነው።
በተያያዘ፥ ከፍተኛ የቤት ግንባታ ማድረግ፤ የሊዝ ዋጋ መቀነስ ይገባል።
የኛ ሀገር ሊዝ እነ ኒዮርክ፣ ለንደን ያስከፍሉታል ከሚባለው አያንስም በሚል ነው የሚተቸው። ስለዚህ በካሬ ሜትር የሊዝ ዋጋ መቀነስና የመሬት አቅርቦቱን ሌሎች አማራጮችን ፈልጎ መፍትሄ ማማጣት ያስፈልጋል።
ያለው ችግር የመኖሪያ ቤት ብቻ አይደለም። የንግድ ቤቶችም በከፍተኛ ዋጋ ነው የሚከራዩት። በከፍተኛ ዋጋ የተከራየ ነጋዴ ባለሱቅ ያንን ዋጋ የሚጭነው ሸማቹ ላይ ነው። ሞሎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሥር ያሉ ሱቆችን ቀድመው የገዙ ሰዎች የሚያከራዩበት ዋጋ ለመስማት የሚዘገንን ነው፤ ይሄ መስተካከል አለበት።
ለንግድ የኪራይ ቤቶችም ታሪፍና የዋጋ ጣሪያ ሊቀመጥ ይገባል " ብለዋል።
በሌላ በኩል ፥ " በአከራዮች ላይ በጣም ስለተጋነነ እንጅ አንዳንድ አከራዮች ደግሞ ልጆች የሚያስተምሩት ባለአንድ መኝታ ቤት ካላቸው ያን አከራይተው፣ ከከተማ ወጣ ያለ ቤት ተከራይተው ነው። የኑሮ ውድነቱ በአከራዩም በተከራዩም ስለሆነ ይህን ችግር ለመፍታት አስታራቂ መፍትሄ ያሻል " ሲሉ አስገንዝበዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ሃምሌ 1 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
ገቢዎች ሚኒስቴር ዛሬ ለጀመረው አዲሱ በጀት ዓመት የግብር ከፋዮች ምደባ (segementation) አድርጓል።
ገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው የግብር ከፋዮች ምደባ በየሦስት አመቱ የሚከናወን መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከሃምሌ 1/2018 ዓ.ም ጀምሮ ግብር ከፋዮች ታክስ የሚከፍሉትም ሆነ ማንኛውንም አገልግሎት የሚያገኙት አዲስ በተመደቡበት ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል ብቻ ይሆናል።
በገቢዎች ሚኒስቴር ስር ያሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችም በአዲሱ ምደባ መሰረት ወደ ቅርንጫፎቻቸው የተመደቡ ግብር ከፋዮችን ዝርዝር ይፋ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የምደባው አስፈላጊነት ምንድነው ? ሲል የገቢዎች ሚኒስቴርን ጠይቋል።
ሚኒስቴሩ በሰጠን ምላሽ የግብር ከፋዮች ምደባ ወይም "ሰግሜንቴሽን" በየሦስት ዓመቱ የሚከናወን አሠራር መሆኑን በመግለጽ፣ ዋና ዓላማውም ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ ሁኔታን መፍጠር መሆኑን ነግሮናል።
"ይህ ምደባ ግብር ከፋዮችን እንደየሥራ ዘርፋቸውና እንደየገቢ መጠናቸው በተመሳሳይ "ክላስተር" እንዲመደቡ ያደርጋል" ያለ ሲሆን ይህም ቅርንጫፎች ለተመደቡላቸው ግብር ከፋዮች እንደየባህሪያቸው ልዩ ድጋፍና አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ብሎናል።
በተጨማሪም የንግድ ተቋማት እያደጉ ሲሄዱ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ደግሞ ወደ ከፍተኛ ግብር ከፋይነት የሚሸጋገሩበት፣ እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴያቸው ሲቀንስ ወደ ታች የሚወርዱበት ሁኔታ መኖሩ ምደባውን አስፈላጊ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግብር ከፋዮች በቅርብ ርቀት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግም የሎኬሽን ወይም የቦታ ምቹነት ታሳቢ ተደርጓል ነው ያለው።
ለዚህም በቅርቡ ሦስተኛው የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በግሎባል አካባቢ መከፈቱ ተጠቅሷል።
ሚኒስቴሩ በሰጠን ማብራሪያ "አንድ ሰው(ግብር ከፋይ) እንደ ንግዱ ባህሪ ባለበት ግብር የመክፈል አቅም ላይ ላይቆይ መቻሉ ፣ንግዱ ሲያድግ ወደ ከፍተኛ ወይም መካከለኛ ፣ መካከለኛው ደግሞ ወደ ከፍተኛ አንዳንዱ ደግሞ እየደከመ ከሄደ ከፍተኛ የተባለው ወደ መካከለኛ ሊወርድ ይችላል ይህም ምደባውን ለማከናወን ሌላው ምክንያት ነው" ብሎናል።
በአሁኑ ወቅትም አዳዲስ የተከፈቱና ነባር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ወደ እነሱ የተመደቡ ግብር ከፋዮችን ዝርዝር ይፋ እያደረጉ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ሃምሌ 1 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
#Tigray : ከማዕከል ራሱን ለይቶ ያዋቀረው የ " ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ሰላማ ከፍተኛ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት " በሁለት አበው ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ያነጣጠረ የግድያ ሙከራ መፈጸሙን አስታውቋል።
ጥቃቱ ያነጣጠረው በብፁዕ አቡነ አረጋዊ እና ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ላይ መሆኑን አመልክቷል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6፡30 ገደማ በአክሱም ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ ነው።
የአክሱም ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በዕለቱ በአበው ሊቃነ ጳጳሳቱ መኖሪያ ግቢ ውስጥ አንድ ጥይት መተኮሱን አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ " ነገሩ ከሚገባው በላይ እየተጋነነ ነው " ብሏል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ገልጿል።
ሃምሌ 1 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
በአዲስ አበባ የ2019 ዓ.ም የቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ ተወሰነ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ እና በኪራይ ገበያው ላይ የሚስተዋሉ መደበኛ ያልሆኑ አሰራሮችን ለመግታት የ2019 በጀት ዓመት የቤት ኪራይ ዓመታዊ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ እንዲጸድቅ መወሰኑን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
ይህ የዋጋ ማስተካከያ ውሳኔ ቀደም ሲል በወጣው የቤት ኪራይ ቁጥጥር አዋጅ መሠረት የተወሰነ ሲሆን፣ በከተማዋ የተካሄደ ሳይንሳዊ ጥናትንና የነዋሪውን የመክፈል አቅም ያገናዘበ መሆኑ ተገልጿል።
ውሳኔው አከራዮች ወቅታዊውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ ፍትሐዊ ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፣ ተከራዮች ደግሞ ካልተገባ የዋጋ ጭማሪና መፈናቀል ድነው የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመላው ከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ-ተከራይ አዲስ የውል ምዝገባና የውል እድሳት ከዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች በይፋ መጀመሩ ቢሮው አያይዞ ገልጿል።
ቢሮው አክሎም፣ " ይህ አሰራር በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው " ብሏል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሃምሌ 1 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
#Iran #USA
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) ፤ " ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ ሶስት የንግድ እና የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የድሮን ጥቃት ፈጽማለች " በማለት እንደ በስትራቴጂካዊ የኢራን ቦታዎች ላይ ከባድ የአየር ድብደባ ፈጽሟል።
የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ዳግም በእጅጉ አገርሽቷል።
ኢራን፣ ዋሽንግተን ኦማን አቅራቢያ አዳዲስ የባህር መስመሮችን ለመክፈት ጥረት እያደረገች እንደሆነና ይህም የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት (MoU) የሚጥስ እንደሆነ ትገልጻለች። ይህ እየተባለ ባለበት ሰዓትና ኢራንም መረከቦች በዛ እንዳያልፉ ባስጠነቀቀችበት ሰዓት ነው ኦማን አቅራቢያ 3 መርከቦች የተመቱ።
አሜሪካም ፣ ለተፈጸመው ጥቃት መላሽ ለመስጠት ወሳኝ ስትራቴጂካዊ የሚባሉ የኢራን ወደብ ቦታዎች ደብድባለች። ከዚህ ወታደራዊ እርምጃ ትንሽ ቀደም ብሎ፣ የአሜሪካው ግምጃ ቤት ለኢራን ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ የነዳጅ ማዕቀብ ማቃለያ በይፋ የሰረዘ ሲሆን ይህም ቴህራን በሕጋዊ መንገድ ነዳጅ ወደ ውጭ የመላክ አቅሟን ያግደዋል።
ኢራን፣ አሜሪካ " የተደረሰውን ስምምነት ጥሳለች " የሚል ክስ እያቀረበችባት ነው።
አሁን ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ዓለም አቀፍ ነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።
ቪድዮ፦ ከማህበራዊ ሚዲያ/ኢራን
ሀምሌ 1 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
#ParliamentQuotes
" የዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊቀር አይችልም 10% እድገት እያመጣን የዋጋ ግሽበትን 0 ማደረግ አንችልም መጠበቅ የለባቹም ፤ ጤናማ በሆነ መንገድ ሲንግድ ዲጂት ከሆነ ከእድገታችን ጋር የሚሄድ ከሆነ አይቀሬ ነው። ችግሩ የሰዎች በገቢያቸው ህይወታቸውን የመደጎም አቅማቸው ውስን መሆን ነው ለዛ ገቢን በሚመለከት በጣም ብዙ ስራ ይጠበቅብናል። የኢትዮጵያን በተለይ በግሉ ዘርፍ ያለውን ትንሹን የደሞዝ መጠን (minimum wage) መመርመር እና ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል። " - ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
#ParliamentQuotes
" ከደመወዙ 35% ግብር ፣ 7% ጡረታ በድምሩ 42% ይቆረጣል። ከ58% ደመወዙ ላይ በእያንዳንዱ በሚሸምተው ሸቀጥ 15% ቫት (VAT) ይቆረጣል። ትራንዛክሽን ላይ ንግድ ባንክ ለሰርቪስና ቫት እያለ ሌሎችም የማይታወቁ ተቆራጮችን ይቆርጣል። ሰራተኛው ለውሃ፣ ለመብራት ለሌሎችም አገልግሎቶች ይቆረጥበታል። እነዚህ ሁሉ ተዳምረው ኑሮን መቋቋም አቅቶታልና ለዚህ ታጋሽ ሲቪል ሰርቪስ እና አነስተኛ ኑሮ ላይ ላለው ዜጋ ምን ታስቦለታል ? ከሚመሰርቱት መንግሥት ምን እንጠብቅ ? " - አቶ ባርጠማ ፍቃዱ
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" 50 ዓመት ፓርቲ መርተህ ፓርቲ የሚተኩ ሰዎች ካልፈጠርክ ሌላ 1000 (ዓመት) ቢሰጥህም አትፈጥርም ማለት ነው ! "
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፦
" የዛሬ 20 እና 30 ዓመት አሁን ያለው መንግሥት፣ አሁን እዚህ ፊትለፊት የምታይዋቸው ሰዎች ከወረዱ በኋላ ተመልሰው መጥተው ኢትዮጵያን እንምራ ካሉ ኢትዮጵያ ሞታለች ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ለዘመኑ፣ ለሲዝን ሚመጥን መሪ መፍጠር ካልቻለች ሰዎች እየወጡ እየወረዱ የሚመላለሱባት ከሆነ ኮሌክቲቭሊ ሞታለች ማለት ነው። ይሄ የሚያኮራ ነገር አይደለም፤ የሚያሳፍር ነገር ነው።
50 ዓመት ፓርቲ መርተህ ፓርቲ የሚተኩ ሰዎች ካልፈጠርክ ሌላ 1000 (ዓመት) ቢሰጥህም አትፈጥርም ማለት ነው።
TPLF 50 ዓመት የፖለቲካ ፓርቲ አንጋፋ ፓርቲ ሆኖ ወጣቱን ትውልድ ማመን ካልቻለ ኪሳራ ነው። በፍጹም አትጠብቁ ድልና TPLF አራምባ እና ቆቦ ናቸው። ለምን መሰላችሁ የሚያሳየው ነገር ፦
- new blood
- new thought
- new direction የማይቀበል ኃይል በነበረው ነገር የትም አይደርስም። ያም ቢሆን እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው።
ከማንም ቢሆን መነጋገር፣ ሰላምና ልማት ነው የምንፈልገው። ከግጭት አናተርፍም፤ አይጠቅመንም።
በተለይ በተለይ ትግራይ አካባቢ የኛ ትልቁ ምኞት ባህርዳር ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ አርባምንጭ የምናየውን የኮሪደር ልማት መቐለ ማየት ነው። ምኞታችን እሱ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው ጉዳይ አጠቅመንም አንፈልገውም። "
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" እርማችሁን አውጡ ! "
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፦
" ... TPLF ምን ጥንካሬ አለው በደምብ ትምህርት ተወስዶበታል ጠቃሚ ስለሆነ ፤ ኦነግ ምን ጥንካሬ አለው ትምህርት ተወድሶበታል ፤ ምን ስንፍናና ድካም አላቸው ትምህርት ተወስዶበታል።
እነሱም በተረጋጋ መንፈስ ያንን መማር ያስፈልጋቸዋል፤ ተከብረው ጥሩ ወላጅ ፣ ጥሩ ሽማግሌ ሆነው መኖር ስለሚቻል። አሁን በስተርጅና ብዙ አስፈላጊ አይደለም።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከእንግዲህ በኋላ አዛውንቶቹን ለምክር እንጂ ለፖሊሲ አመጪነት አይፈልግም።
እውነቴ ነው ፤ ምክር ብቻ ነው ! ምክንያቱም ዓለም ተገለባብጣለችና አሁን ያለችውን ዓለም እናተ ለመገንዘብ በጣም በጣም ከባድ ስለሆነ አልፎ አልፎ ምክር ሲያስፈልግ ከሁሉም ሽማግሌዎች መስማት ጥሩ ነው፣ ማክበር ጥሩ ነው፣ ሲታመሙ ማሳከም ጥሩ ነው ፣ ከሞቱም በክብር መቅበር ጥሩ ነው ፤ ከዛ አልፎ ግን ፖሊሲ እንዲያመነጩ እኔም አልጠብቅም ከኔ በላይ ያላችሁም እርማችሁን አውጡ፤ ጊዜው እያለፈ ነው። "
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" በየቀኑ በርካታ ውጊያ፣ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ፕሮቮኬሽንስ (ትንኮሳዎች) በየጊዜው በትግራይ ባሉ ኃይሎች ይፈጸማል፣ በየጊዜው " - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ሲሆን በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ጉዳይ የተመለከተም ምላሽ ሰጥተዋል።
በምላሻቸው "በየቀኑ በርካታ ውጊያ፣ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ፕሮቮኬሽንስ (ትንኮሳዎች) በየጊዜው በትግራይ ባሉ ኃይሎች ይፈጸማል፣ በየጊዜው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዛም ባለፈ በከፋ መልኩ "በርካታ የትግራይ ልጆች በጉልበት ታፍሰው ሱዳን ላለው ጦርነት ተሸጠዋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በሱዳን ጦርነት ውስጥ የትግራይ ወጣቶች በማያውቁት ጉዳይ ህይወታቸውን እያጡ ነው" ብለዋል።
በዝርዝር ምን አሉ?
" ከሁሉ የከፋው አሁን በርካታ የትግራይ ልጆች በጉልበት ታፍሰው ሱዳን ላለው ጦርነት ተሸጠዋል።
በሱዳን ጦርነት ውስጥ የትግራይ ወጣቶች በማያውቁት ጉዳይ ህይወታቸውን እያጡ ነው የሚገኙት። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጉዳይ አልበቃ ብሎ ጉዳዩ ወደ ሱዳን ተሸጋግሯል።
በዚህ ሁሉ ውስጥ የትግራይ ህዝብ ተጎጂ ነው የትግራይ ህዝብ የችግሩ ባለቤት ሳይሆን የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነው የትግራይን ህዝብ ችግር የበለጠ ያባባሰው የውስጥ ቁስል መሆኑ ነው፤ የማይታይ የውስጥ ቁስል በቀላሉ የማይሽር መሆኑ ነው።
ዛሬ በትግራይ ውስጥ ከሚኖር ትግራዋይ በላይ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚችል፣ አፈሳ የማይካሄድበት፣ በደሴ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ አርባምንጭ፣ ሐዋሳ ያለው ትግራዋይ ትግራይ ካለው ሰው በላይ ሰላም አለው። ትግራይ ካለው ሰው በላይ በሰላም ወጥቶ መግባት ይችላል።
የሚያሳዝነው የዚህ ጉዳይ ትግራይ ብቻ አይደለም። አማራ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለአማራ ህዝብ ሰላም፣ ደህንነት፣ ጥቅም እንታገላለን ብለው የሚሉ ኃይሎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ካለው የአማራ ተወላጅ ይልቅ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ ያለው አማራ ሰላም አለው። እነዚህ 'ልታገልልህ' የሚሉ ኃይሎች ያሉበት አካባቢ የበለጠ ፍራቻ፣ የበለጠ ግድያ፣ የበለጠ ዘረፋና መታገዶች አሉ።
ኦሮሚያ አካባቢ ለኦሮሞ እንታገላለን ብለው የሚምሉና የሚገዘቱ ኃይሎች ከሚንቀሳቀሱበት አካባቢ በላይ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀስ፣ በሶማሌ የሚንቀሳቀስ፣ በአፋር የሚንቀሳቀስ ኦሮሞ የተሻለ ሰላም አለው።
ዜጎች በገዛ ቀያቸው፣ በመንደራቸው፣ በገዛ ልጆቻቸው እየታመሱ ይገኛሉ። ከቀያቸው ሸሽተው መኖር የተሻለ ሰላም የሚያገኙበት እየሆነ መጥቷል። ከህዝብ ተነጥሎ፣ ህዝብ አስለቅሶ፣ ህዝብ ዘርፎ የሚደረግ ትግል ደግሞ የትም ማድረስ እንደማይችል ከታሪኮቻችን መማር የምንችል ይመስለኛል።
መንግስት አብዛኛውን ጉዳይ በትዕግስት የሚያየው፣ ወደ ግጭት የማይገባው ለምንድን ነው ያላችሁ እንደሆነ አላማ ቢስ ነው አላማ የለውም ይህንን ግጭት ከፈጸምን በኋላ አሳካን ብለን የምንናገረው አንዳች ቁምነገር የለም በዚህም በዚያም ብንገድል ብንሞት ትርጉም የለውም።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ትግራይ አካባቢ ያለው የፖለቲካው አውድ የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ ነው ትግራዋይና ኢትዮጵያውያን የሆኑት።
መጥረቢያ ሶስት አክተሮች አሉት አንደኛው አክተር ከ ብረት የሚሰራው የሚቆርጠው የተሳለ ነገር። ሁለተኛው አክተር ተጣጥሞ እዛ ውስጥ የሚገባው እንጨት ነው። ሶስተኛው አክተር እንጨቱን ይዞ የሚቆርጠው አካል ነው።
የመጀመሪያው ብረት የተሳለ መጥረቢያ ምንም አላማ የለውም የእጁን አላማ ይፈጽማል እንጨቱን ሲያዘው ብቻ የእንጨቱን ፍላጎት፣ የእንጨቱን አላማ ፈጻሚ እንጂ የራሱ ሀሳብ የራሱ አላማ የለውም።
እንጨቱም የያዘውን እጅ ወደ መራው የሚሄድ፣ በያዘው እጅ የሚታዘዝ፣ የያዘውን እጅ ፍላጎት የሚመልስ እንጂ የራሱ አላማ የለውም ህወሓት እንደ መጥረቢያ ነው፤ መያዣው እንጨት እንደ ሻዕቢያ ነው ዋና አዛዦች ባለጉዳዮች ሌሎች ናቸው።
ከመጥረቢያው ጋር ከብረቱ ጋር ብንጋጭ እንጨቱ እስካለ ድረስ፣ ከእንጨቱ ጋር ብንጋጭ እንጨቱን የሚያዘው ሰው እስካለ ድረስ ዘላቂ ሰላም አናገኝም።
ይልቁንስ ለመጥረቢያውና ለእንጨቱ ያለኝ ምክር የኢትዮጵያ ሰላምና እድገት የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋችኋል፤ የሚልካችሁ አካል መጠቀሚያ ያደርጋችኋል እንጂ ምንም ፋይዳ የለውም የሚል ሲሆን፣
በእኛ በኩል ግን ዝግጅቱ ኢትዮጵያ የሰላሟ መደፍረስ ምንጭ የት እንደሆነ ስለምናውቅ ከምንጩ የሚነሳውን ማንኛውንም ትንኮሳ ለመከላከል የሚያስችል ቁመና በመፍጠር ላይ የምንገኝ መሆኑን ለተከበረው ምክር ቤት መግለጽ እፈልጋለሁ።
የኢትዮጵያ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት አደጋ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ማንኛውም ነገር ከመጣ ለመከላከል የሚያስችል ቁመና እንዳለን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።
መጥረቢያውና መያዣውን እንጨት ግን በተቻለ መጠን መታገስ፣ በተቻለ መጠን ማስተማር፣ በተቻለ መጠን መመለስ ያስፈልጋል ጉዳቱ የጋራ ስለሚሆን።
ታስታውሱ እንደሆነ ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት የነበረው የፖለቲካ ዲስኮርስ 'ኢትዮጵያ አለቀላት፣ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው፣ ኢትዮጵያ ልትወድቅ ነው' የሚል ነበረ።
'ኢትዮጵያ አትወድቅም' ብዬ በተደጋጋሚ አነሳላችሁ ነበር።
'ኢትዮጵያ አትወድቅም' አይደለም አሁን የምላችሁ፤ የወደቁት ታነሳለች። የወደቁት ታነሳለች፣ የተኙትን ታነቃለች፤ ሊለሙ ሲገባቸው ያልገባቸውን ወንድምና እህቶቿን አንቅታ ወደ ብልጽግና ጎዳና ትወስዳለች። ይህ የኢትዮጵያ ጉዞ ይሆናል " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
#NationalDialogue🇪🇹
" ለእኔ ሳይሆን ለእኛ፣ ለሰፈሬ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ማለት ከቻልን ይህ ምክክር ፍሬያማ ይሆናል" ሲሉም አሳስበዋል " - ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)
👉 " ይህ ጉባኤ በቀላሉ የማይደገም ነው ! "
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደጋግሞ የሚታየውንና በኃይለቃል ጀምሮ በኃይል እርምጃ የመደምደም የፖለቲካ ስብራት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በሀገራዊ የምክክር ጉባዔ የመክፈቻ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠ/ሚኒስትሩ፥ በቀጣዮቹ ሳምንታት ከ4 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን የሚያሳትፈው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ የምትጽፍበት "የብዕርና የብራና" ታሪካዊ አጋጣሚ ሲሆን፣ በቀላሉ የማይደገምና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ግዙፍ ዓላማ ያለው መድረክ መሆኑ ተናግረዋል።
" አንዳንድ አጋጣሚዎች ከታሪክ ብዕርና ብራና ፊት ያቆማችኋል፤ ዛሬ የምንገኝበት መድረክም ሀገርን የሚጠቅምና ለዘመናት የሚታወስ ታሪክ ለመጻፍ ዕድል የሚሰጥ ነው " ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በኃይለቃል ተጀምሮ በኃይል እርምጃ የሚደመደምበትን አዙሪት በንግግርና በውይይት የመተካት ወቅት ላይ እንደተደረሰም ገልጸው፣ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።
ተወያዮች ከአካባቢያቸው ወጥተው ለኢትዮጵያ፣ ለዛሬ ሳይሆን ለነገ፣ ለራሳቸው ሳይሆን ለልጆቻቸው እንዲመክሩም ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚያነሱትን ጥያቄ በመደማመጥ እና ማንም ሳይጎዳ በጋራ መጠቀም የሚያስችሉ መፍትሔዎችን መፈለግ የምክክሩ ስኬት መሠረት እንደሚሆን ገልጸዋል።
" ለእኔ ሳይሆን ለእኛ፣ ለሰፈሬ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ማለት ከቻልን ይህ ምክክር ፍሬያማ ይሆናል" ሲሉም አሳስበዋል።
ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)፥ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ የሰላም፣ የተስፋና የመደማመጥ ባህል መገንባት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፣ በሀገር ውስጥ በሚደረግ ውይይትና በይቅርታ ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያን ከውጭ ጣልቃ ገብነት መጠበቅ እንደሚቻል ገልጸዋል።
(ሙሉ ንግግራቸው ከላይ ተያይዟል)
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ሃምሌ 8 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" 100% በአንድ ጊዜ የሚጭምሩ አከራዮች አሉ። ከ100% በላይ የሚጨምር አለ። ይሄ በፍጹም ስግብግብነት ነው " - ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የቤት ኪራይ በተመለከተ አጠናሁት ያለው ጥናት የአከራይን መብት " ከግምት ውስጥ ያላስገባ " እና ተጨማሪ ጊዜና ሀብት ያባከነ የሚል ትችት ቀርቦበታል።
ይህ የተባለው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ማጠቃለያ ጉባዔ በተካሄደበት መድረክ ሲሆን የም/ቤት አባላት ካነሷቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል ከሰሞኑ የወጣው የ11.5% የቤት ኪራይ ጨማሪ ጉዳይ ይገኝበታል።
የምክር ቤት አባሉ ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)፣ " አከራይና ተከራይን በተመለከተ የወጣው ህግ ክፍተቶች ያሉበት፣ ህብረተሰቡን በማወያየት የአከራዩንም የተከራዩንም ስሜትና ፍላጎት በማገናዘብ አማካኝ የሆነ ነገር ይዞ ያልወጣ " ብለውታል።
በቀረበው ሪፖርት ከ500 ሺሕ በላይ የአከራይና ተከራይ ግንኙነቶች እንዳሉ መስፈሩን፣ ይህም በአባወራ ደረጃ መሆኑን ጠቅሰው፣ " በስሩ አራት ሰዎች አሉ ብለን ከወሰድን 2 ሚሊዮን ህዝብ ነው። ስለዚህ በዚህ ደረጃ ክብደት ሰጥተን ማየት አለብን " ሲሉ አፈጻጸሙ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።
አከራይና ተከራይን የተመለከተው ህግ በየዓመቱ የኪራይ መጠን እየተጠና እንዲጨመር ያስቀምጣል ያሉት ሲሳይ (ዶ/ር)፣ " ዘንድሮ ተጠና ተብሎ የቀረበው ጭማሪ በሁለት አመቱ ነው። ስለዚህ አዋጁ ለአከራዮች የሰጠውን መብት እንኳ እየነፈግን ነው " ሲሉ ተናግረዋል።
" የተከራዮች ብቻ ሳይሆን የአከራዮችን መብትም ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል። ግንኙነታቸው ሰላማዊ እንዲሆን " ብለዋል።
" የእንጨት የነበረን ቤት አሻሽሎ በብሎኬት ሰርቶ አከራዩ ኪራይ እንዲጨምር የሚያደርግ አሰራር አለ ወይ ? ለእድሳት ላወጣው ወጭ ለማካካስ የኪራይ ጭማሪ ማድረግ ይችላል ? " ሲሉም ጠይቀዋል።
የ2019 ዓ/ም የቤት ኪራይ ጭማሪ 11.5% እንዲሆን የተወሰነበት ጥናት የማዕከላዊ ስታቲክስ (CSA) ካወጣው ጥናት (ዓመታዊ የዋጋ ጭማሪ ከ10 እስከ 13%) ተመሳሳይ ስለሆነ ከዛ መውሰድ እየተቻለ ተጨማሪ ጥናት በማድረግ ጊዜና ሀብት ባክኗል ፤ ይህም አስፈላጊ አይደለም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ደግሞ፣ " ጥናቱ ሳይንሳዊ ነው " በማለት ሌላ ከማጥናት ይልቅ " የCSA ጥናት ቢወሰድ ተመሳሳይ ነው " መባሉን " ተመሳሳይ አይደለም " የሚል ምላሽ ሰጥተውበታል።
" CSA የሚያጠናው ጥናት ሀገራዊ ነው፤ እኛ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለውን ችግር መሰረት አድርገን ነው ያጠናነው " የሚል መሞገቻም አቅርበዋል።
የጥናቱ መስፈርቶች ፦
- የCSAን ጥናት፣
- የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተተት (30%)
- የዜጎች የመክፈል አቅም (15%)
- የቤት ጥገና እና ማሻሻያ ወጭ (15%)
- ከተማ ላይ ያለ የህዝብ ብዛት ለወጥ፤ ታሳቢ ተደርጎ ከ100% ተይዞ የተጠና መሆኑን ቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ምን አሉ ?
" በተጨማሪ አጠናን በአጋጣሚ እርስዎ (ዶ/ር ሲሳይ መንስግስቴ) እንዳሉት ሆነ። የቤት ኪራይ መጨመር ግድ የሚልበት ሁኔታ ካለ እስከ 11.5% ድረስ እንዲሆን ጣሪያውን ነው የሚያስቀምጠው፤ ከዚያ ማለፍ አይቻልም።
በከተማችን ባደረግነው ጥናት 100% በአንድ ጊዜ የሚጭምሩ አከራዮች አሉ። ከ100% በላይ የሚጨምር አለ። ይሄ በፍጹም ስግብግብነት እንጅ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይና ለዚያ ተብሎ የሚደረግ እንዳልሆነ አይተናል።
ተከራይን ከቤት ለማስወጣትም ሲፈለግ ተመሳሳይ ድርጊት እንደሚፈጸም አይተናል። ህጉ የተከራዩንም የአከራዩንም መብት የሚጠብቅ ሁሉንም ወገን ያማከለ አሰራር ስለሆነ በአሰራር ስርዓቱ መግባት ግድ ይላል።
በደረስንበት ልክ ህጉ ላይ ያልገቡትን ግን ህጉ ላይ በተቀመጠው መንገድ እየቀጣን ማስተካከያ እያደረግን የምናስተገብር ይሆናል " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
@tikvahethiopia
#እንድታውቁት
#AddisAbaba
ከለሊት 11:30 ጀምሮ መንገዶች ይዘጋሉ።
ነገ ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ/ም በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስተባባሪነት የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ይደረጋል።
ውድድሩ መነሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ለገሀር፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ንግድ ባንክ፣ ጋንዲ ሆስፒታል ፣ ጊዮን ሆቴል በማድረግ መስቀል አደባባይ ፍጻሜውን ያነኛል።
ውድድሩ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ፦
- ከኦሎምፒያ አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ (ኦሎምፒያ አደባባይ)
- ከጥላሁን አደባባይ ወደ ሳንጆሴፍ መብራት (ጥላሁን አደባባይ) ለከባድ ተሽከርካሪ አጎና ሲኒማ
- ከAU መብራት ወደ ሜክሲኮ አደባባይ (ጥይት ቤት መስቀለኛ)
- ከፓርላማ መብራት ወደ ኮንሰን መታጠፊያ (ፓርላማ መብራት)
- ከኮንሰን መታጠፊያ ወደ ገብርኤል (ኮንሰን መታጠፊያ)
- ከጥይት ቤት ወደ ገብርኤል በጀርባው (ጥይት ቤት መታጠፊያ)
- ከሴቶች አደባባይ ወደ ካዛንቺስ (ሴቶች አደባባይ)
- ከሴቶች አደባባይ ወደ ካዛንቺስ ቶታል (ሴቶች አደባባይ)
- ከ22 አደባባይ ወይም ዘሪሁን ህንፃ ወደ ዑራኤል አደባባይ (ዘሪሁን ህንፃ መስቀለኛ)
- ከጋዜቦ አደባባይ ወደ ደንበል (ጋዜቦ አደባባይ ላይ)
- ከቂርቆስ ቤ/ክርስቲያን መስቀለኛ ወደ ለገሃር መብራት (ቂርቆስ ቤ/ክርሰቲያን ነርክ ተራ)
- ከላንድ ማርክ ሆስፒታል መታጠፊያ ገነት ሆቴል ወይም ወደ ገነት መብራት (ላንድ ማርክ ሆስፒታል መስቀለኛ)
- ከጠማማ ፎቅ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ (ጠማማ ፎቅ መስቀለኛ)
- ከAU መብራት ወደ ሜክሲኮ አደባባይ (ሜክሲኮ ጥይት ፋብሪካ መስቀለኛ)
- ከከፍተኛ ፍ/ቤት አደባባይ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ (ከፍተኛ ፍ/ቤት አደባባይ)
- ከሠንጋ ተራ 40/60 ወደ ሠንጋ ተራ መብራት (ሠንጋ ተራ 40/60 መታጠፊያ)
- ከጎማ ቁጠባ መብራት ወደ ብ/ቲያትር (ጎማ ቁጠባ መብራት)
- ከሜትሮሎጂ መታጠፊያ ወደ ፖስታ ቤት መብራት (ሜትሮዎሎጂ መታጠፊያ )
- ከጥቁር አንበሳ ሼል ወደ ኢምግሬሽን (ጥቁር አንበሳ ሼል)
- ከጎላ ሚካኤል መስቀለኛ ወደ ኢሚግሬሽን (ጎላ ሚካኤል መስቀለኛ)
- ከአገር አስተዳደር መብራት ወደ ብሔራዊ ቲያትር (አገር አስተዳደር መብራት)
- ከንግድ ማተሚያ ወደ ኦርማ ጋራዥ (ንግድ ማተሚያ መስቀለኛ) ... እሁድ ከለሊቱ 11:30 ሰዓት ጀምሮ እስከ ፕሮግራሙ ፍፃሜ ድረስ እንደሚዘጋ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አሳውቋል።
በተገለፁት መስመሮች ላይ መኪና ለአጭርም ይሁን ለረጅም ጊዜ ማቆም ተከልክሏል።
ሐምሌ 4 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
🎓" ከ2010 ዓ/ም እስከ 2015 ዓ/ም የዲግሪ ተመራቂዎች በሙሉ የትምህርት ማስረጃቸውን ለማረጋገጥ በድጋሚ ፈተና ሊፈተኑ ነው " በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ የተሳሳተና ህዝብ አደናጋሪ ነው።
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች (በፌስቡክ እና ቲክቶክ) ላይ የኢፌዴሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ያዘጋጀውንና ለህዝብ አስተያየት ይፋ ያዳረገውን አዲስ ረቂቅ መመሪያ በማዛበት፣ " ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተና ሳይፈተኑ በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ የተመረቁ ተማሪዎች በሙሉ የትምህርት ማስረጃቸውን ለማረጋገጥ ሲባል በድጋሚ ፈተና ሊሰጣቸው ነው " በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍጹም የተሳሳተ እና ህዝብን የሚያደናግር ነው።
የህዝብ አስተያየት እንዲሰጥበት ይፋ የተደረገው መመሪያ በትክክል እነማንን ነው የሚመለከተው ?
ይህ መመሪያ/አሰራር የሚመለከተው በቀድሞው ዲፕሎማ (10+3፣ 12+2 ወይም ቴክኒክና ሙያ ደረጃ 4 ስልጠና) ተመርቀው፣ ነገር ግን የደረጃ አራት የብቃት ማዕቀፍ (COC) ሳይኖራቸው የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪ (MA) ወይም ሦስተኛ ዲግሪ (PhD) የያዙትን ብቻ ነው።
እነዚህ ዜጎች የትምህርት ማስረጃቸውን ለማረጋገጥ አሁን በያዙት የትምህርት ደረጃ/የያዙት ዲግሪን መሰረት ተደርጎ የሚሰጠውን ፈተና መውሰድና ማለፍ ይኖርባቸዋል።
በአጭሩ የሚመለከተው ወይም ተፈጻሚነቱ :-
- ለዲግሪ ትምህርት ከመግባታቸው በፊት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ (COC) ፈተና ሳይወስዱ ዲግሪ የተማሩ እና የተመረቁ።
- የሙያ ብቃት ማረጋገጫ (COC) የወሰዱት ለዲግሪ ትምህርት ከተመዘገቡ በኋላ የሆኑ ተማሪዎች ላይ ነው።
በመደበኛው መንገድ የመግቢያ መስፈርቱን አሟልተው (ለምሳሌ የ12ኛ ክፍል ማለፊያ አምጥተው) የገቡ፣ ወይም ከዲፕሎማ ተነስተው የCOC ፈተና አልፈው ዲግሪ የጫኑ እና የተመረቁ ዜጎችን ይህ መመሪያ አይመለከታቸውም። የትምህርት ማስረጃቸውም ያለ ምንም ተጨማሪ ፈተና እንደ ቀድሞው ይረጋገጥላቸዋል።
መመሪያው በአሁኑ ወቅት በረቂቅ ደረጃ ላይ ያለና እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለህዝብ አስተያየት ክፍት የተደረገ መሆኑ ታውቋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ሃምሌ 4 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" አስፈላጊው በጀት እንዲመጣ ተደርጎ ተማሪዎቹ በግቢው እንዲቆዩ ተደርጓል " - አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎች፣ በክልሉ አለ ባሉት " አስገዳጅ የውትድርና ምልመላ " እና የጸጥታ ስጋት ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ እንደማይችሉ ገልጸው፤ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የክረምት ማደሪያ (ዶርሚተሪ) እንዲፈቅድላቸው በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ተማሪዎቹ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በላኩት አቤቱታቸው፤ ወደ ክልሉ መመለሳቸው ከአካላዊ ደህንነት ስጋት ባለፈ፣ የጀመሩትን የከፍተኛ ትምህርት ጉዞ ሙሉ በሙሉ ሊያቋርጥባቸው እንደሚችልም መግለጻቸው ይታወሳል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ክረምቱን እንዲያሳልፉ የተፈቀደላቸው መሆኑን ከተማሪዎቹ ሰምቷል።
ተማሪዎቹ ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ እስከሚቀጥለው የትምህርት አመት ድረስ አስፈላጊውን የምግብ እና የዶርም አገልግሎት እያገኙ በግቢው እንዲቆዩ የተፈቀደላቸው መሆኑን ገልጸውልናል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምዩኔኬሽን ዳይሬክተር ኤልያስ ወርቁ (ዶ/ር) ይህንኑ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።
ዳይሬክተሩ " አስፈላጊው በጀት እንዲመጣ ተደርጎ ተማሪዎቹ በግቢው እንዲቆዩ ተደርጓል" ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄይሉ ኡመር (ዶ/ር) ተማሪዎቹ በግቢው ያሉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ላቀረቡት ቅሬታም ምላሽ የተሰጠ መሆኑን በማረጋገጥ አስፈላጊው ነገሮች እየተደረጉ ይቆያሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ያቀረቡት ቅሬታ ደርሷቹ ነበር ? በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ከትግራይ ክልል መጥተው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎችስ ጉዳይ? ስንል ጠይቀናል።
በምላሻቸው እስካሁን ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህን አይነት ቅሬታ አለመድረሱን ገልጸው መሰል ቅሬታዎች ካሉ የሚያጣሩ መሆኑን አሳውቀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሃምሌ 3 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" አንድ ሊትር ሲሰጡ/ሲቀዱ ሙሉ አንድ ሊትር አይደለም መለኪያው " - የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን (ለቲክቫህ ኢትዮጵያ)
👉 " ማደያዎች ላይ ነዳጅ እንዳያቀርቡ እርምጃ ስለተወሰደ አቅርቦቱ ላይ ችግር አይፈጥርም! "
የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን፣ ከግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ ከተሞች "ድንገተኛ የኢንስፔክስን ስምሪት በነዳጅ ማደያዎች የመቅጃ ማሽን (ዲስፔንሰር) ላይ ምርመራ በማድረግ 12 ማደያዎች ማሽኖቻቸው ትክክለኛውን ልኬት የማያሳዩ እና የነዳጅ ቅሸባ የሚፈጸምባቸው መሆኑን" ማረጋገጡን ዛሬ አሳውቋል።
ባለስልጣኑ ማደያዎቹ "ከሰኔ 23/2018 ዓ/ም ጀምሮ እንደ ጥፋታቸው መጠን ከአንድ እስከ ሁለት ወር የነዳጅ ጭነት ዕገዳ" እንደተደረገባቸውም ገልጿል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ስለጉዳዩ የተጠቃቸው የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር)፣ " አንድ ሊትር ሲሰጡ/ሲቀዱ ሙሉ አንድ ሊትር አይደለም መለኪያው። 800፣ 900 ሚሊ ሊትር ይሆናል። ለትነት የሚፈቀድ መገጠን አለ፤ ከዚያ በላይ መቀሸብ ህገወጥነት ነው " ብለዋል።
ማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል እንዳልሆነም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፥ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ባለስልጣኑ የወሰደው እርምጃ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ፣ ነዳጅ እንዳያቀርቡ እርምጃ መውሰዱ በማደያዎች ላይ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ሲቀዱ ከእስከዛሬው የበለጠ መስተጓጎል እንዳያስከትል የቅጣቱ አይነት ከዚህ የተለየ ቢሆን የሚል አስተያየት ሲሰጡ ተስተውለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ ከነዳጅ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ተሽከርካሪዎች ማደያ ላይ መጉላላት እንደሚገጥማቸው በተደጋጋሚ ቅሬታ ይቀርባል፤ የተወሰደው እርምጃ ነዳጅ በሚቀዱ ተሽከርካሪዎች ላይ መጉላላትን አያስከትልም ወይ ? ከምን አንጻር ታስቦ የተወሰደ እርምጃ ነው ? ሲል ባለስልጣኑን ጠይቋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር)፣ እርምጃው " መጉላላት አይፈጥርም " ሲሉ መልሰዋል።
" እርምጃ በተወሰደባቸው ማደያዎች ምክንያት ምንም አይነት ችግር አይፈጠርም " ነው ያሉት።
አክለውም ፣ " ገና በአቅርቦት ላይ ችግር ይፈጠራል ተብሎ ህገወጦችን መደበቅ ተገቢነት የለውም " ብለዋል።
" የማደያ ችግር አይደለም ያለው " ያሉት ደስታው (ዶ/ር)፣ " እርምጃ በተወሰደባቸው ማደያዎች ዙሪያ ሌላ ማደያ አለ። ቢያንስ አንድ፣ ሁለት ወይም ሦስት ይኖራል " ሲሉ ገልጸዋል።
ለምሳሌ፣ " አዲስ አበባ ላይ ወደ 130 ማደያ ነው ያለው። አራት፣ አምስት ማደያዎች ላይ (ነዳጅ እንዳያቀርቡ) እርምጃ ስለተወሰደ አቅርቦቱ ላይ ችግር አይፈጥርም፤ ሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ነው የሚሆነው " ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
" ችግር ያለባቸው ከድርጊታቸው እንዲታረሙ ነው እርምጃ የምንወስደው። እስካሁን በወስድናቸው እርምጃዎች በጣም Critical የሆነ የአቅርቦት ችግር ያለበት የለም። ምክንያቱም በአንድ ከተማ ውስጥ ከሦስት፣ አራት በላይ ማደያ ነው ያለው " ብለዋል።
"ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቅሬታ የቀረበው አሁን በቅርቡ ነው። እኛ ኦፕሬሽን የምንሰራው በተደጋጋሚ ነው። ግንቦት 29 ነው የሚለው ደብዳቤው እንዳየኸው። በቅርቡ ነው ልክ የኢንስፔክሽን ስራው ሲጀመር ማስጮህ የተጀመረው " ሲሉ ተናግረዋል።
" እርምጃ የተወሰደባቸው በቀጣይም ቀናት ይፋ የሚደረጉ ሌሎች ማደያዎች አሉ " ሲሉም የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ስንት እንደሆኑ ስንጠይቃቸው " በተቋሙ የፌስቡክ ገጽ ነው የሚገለጸው " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ሃምሌ 1 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ከቀጥተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ።
ባለፉት 5 ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠንካራ ተቃዋሚነታቸውና በደፋር ተናጋሪነታቸው የሚታወቁት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ከማንኛውም ቀጥተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ማግለላቸውን በይፋ አስታወቁ።
በትላንትናው ዕለት የፓርላማ ቆይታቸውን ያጠናቀቁት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ከማንኛውም ፓርቲ አባልነትም ሆነ ደጋፊነት መውጣታቸውን ገልጸዋል።
ደሳለኝ (ዶ/ር)፤ "በትናንትናው የምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'አብረን እንስራ' በማለት ላቀረቡልን ጥሪና ላሳዩን አክብሮት ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።
" ከጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ ጥያቄ ያቀረብን የተቃዋሚ የምክር ቤት አባላት ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረን የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ላይ፣ በ7ኛው ዙር ምርጫ በባሕር ዳር ከተማ ለመወዳደር ተመዝግቤ ቢሆን ኑሮ እጩ ላለማቅረብ ወስነው እንደነበር ገልጸውልኛል " ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር)፤ " በምክር ቤቱ ሳነሳቸው የነበሩ ሀሳቦች ጠቃሚ እንደነበሩ፣ በትኩረት እንደሚወስዷቸው እና በምክር ቤቱ ብቀጥል ፍላጎታቸው እንደነበር የገለጹልኝን ሀሳብም በበጎ ጎኑ እና በቅንነት ተመልክቼዋለሁ " ሲሉ ገልጸዋል።
ደሳለኝ (ዶ/ር) ላለፉት 10 ዓመታት የሕዝብን አደራ ለመወጣት ካደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ድካም በኋላ፣ አሁን ላይ ትኩረታቸውን በሙያቸው ሀገራቸውን ማገልገል፣ ጎን ለጎን ወደ ግሉ ዘርፍ በመግባት በፈጠራ ሥራዎች (Startups) ላይ መሰማራት እና ለቤተሰባቸው ጊዜ መስጠት ላይ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ቀጥተኛ ፖለቲካውን ቢሰናበቱም፣ የአማራን ሕዝብ አንድነትና ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር ያለውን አብሮነት በሚያጠናክሩ ማኅበራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሙያቸው ማገዛቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠው፤ አዲሱ የ2019 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የእውነተኛ ሰላምና የተስፋ ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ወደ ፖለቲካው ከመግባታቸው በፊት በነበራቸው የዩኒቨርሲቲ መምህርነት ሕይወታቸው እንዲሁም የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ በአክቲቪዝም እና የሀገር በቀል ሲቪክ ማኅበራትን በግንባር ቀደምትነት በመምራት ሰፊ የማኅበረሰብ አገልግሎት በማበርከት ይታወቃሉ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
@tikvahethiopia
" ዋጋ ጭማሪውና የውል እደሳቱ መነሻ የሚሆነው ከዚህ ቀደም በነበረው ውል ላይ የተቀመጠው የኪራይ ዋጋ ብቻ ነው " - ቢሮው
በ2019 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ፣ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ የጸደቀ ሲሆን ሕገ-ወጥ " የመንደር እና የአካባቢ ውሎች " በጥብቅ ተከልክለዋል።
ዋጋ ጭማሪውና የውል እደሳቱ መነሻ የሚሆነው ከዚህ ቀደም በነበረው ውል ላይ የተቀመጠው የኪራይ ዋጋ ብቻ መሆኑን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡
በመላው ከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ-ተከራይ አዲስ የውል እድሳት ምዝገባ ከዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ መተግበር መጀመሩ ተገልጿል።
የተጣሉ ጥብቅ ክልከላዎች ምን ምን ናቸው ?
አዲሱን የውል እድሳት ምዝገባና የተቀመጠውን የዋጋ ጣሪያ ወደ ጎን በመተው የሚፈጸሙ ማናቸውም ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ ጥብቅ ክልከላ ተጥሏል።
በዚህም መሠረት ፡-
- በቢሮው ከተመዘገበው እና ከሚመዘገበው ውል እንዲሁም ከሚሰጠው አቅጣጫ ውጭ፣ «ልዩ ውል» በሚል የሚፈጸሙ ማናቸውም የመንደር ውሎች፤
- ከሕጋዊ አሰራር ውጭ የሚደረጉ የአካባቢ ውሎች፤
- በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) አካባቢ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ውሎች ሙሉ በሙሉ የተከለከሉ ናቸው።
ማንኛውም አከራይ እና ተከራይ እነዚህን የተከለከሉ ሕገ-ወጥ ውሎች ይዘው ሲገኙ ወይም ከተቀመጠው የ11.5% የዋጋ ጭማሪ ጣሪያ በላይ ፈጽመው ከተገኙ ቢሮው ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስጠንቅቋል።
ሃምሌ 1 ቀን 2018 ዓ/ም
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
📱ድንገት ዳታዎ ቢያልቅብዎት አይጨነቁ! አሁኑኑ ወደ *711# በመደወል የ1.5 ጊባ የዕለታዊ ጥቅል ክሬዲት በ60 ብር ብቻ ያግኙና መጠቀምዎን በደስታ ይቀጥሉ።
#SafaricomEthiopia #FurtherAheadTogether
#ParliamentQuotes
" በቅርቡ ጥናት አጥንተን ነበር። ከግማሽ በላይ ከ50% በላይ የሙስሊም ማህበረሰብ ያለባቸው ወረዳዎች አብዛኛው ሙስሊም የሆነበት ወረዳዎች 1,263 ቤተክርስቲያኖች አሉ፤ አብዛኛው እስላም የሆነበት አካባቢ ፤ ከ1 ሺህ ውስጥ ስንት ቦታ ነው ግጭት የምንሰማው ነው አሁን ? የሃይማኖት ግጭት ካለ አብዛኛው ሙስሊም ያለበት አካባቢ ሁሉም ቦታ ግጭት ይጠበቅ ነበር ፤ ግን የእስልምና ባህሪ ግጭት አይደለም ፤ የክርስትና ባህሪ ግጭት አይደለም። ክርስቲያኖች የበዙባቸው አካባቢዎችም እንደዚሁ መስጂዶች አሉ የምንሰማው ችግር ግን ጥቂት ቦታ ነው። በዚህ ሁሉ ስፋት ችግር አንሰማም። አስተውላችሁ ከሆነ ነውጠኞች ክብሪት ፣ ጭድ ይዘው ይለኩሳሉ። ጀሌዎቻቸው እዚሁ አዲስ አበባ ተቀምጠው ቤንዚን እያርከፈከፉ እሳቱን ያራግቡታል። ለኳሽ እና አራጋቢ ማዶ ለማዶ ተቀምጠው ችግሩን የእምነት ፣ የብሄር መልክ ለመስጠ ይሞክራሉ። " - ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
#ParliamentQuotes
" ቋሚ ደሞዝ የሚከፈላቸው የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች፣ አነስተኛ ነጋዴዎች፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ወገኖቻችን በስውር ረሀብ ውስጥ ወድቀዋል። የቤት ኪራይ ከአብዛኛው ዜጎቻችን ወርሃዊ ገቢ በላይ ሆኗል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን መካከለኛ የሚባል የህብረተሰብ መደብ ጠፍቶ ጥቂት እጅግ የበለፀጉ እና አብዛኛው በድህነት የሚማቅቅ ሁለት መደቦች ሆነዋል። " - ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
ፎቶ/ቪድዮ ፦ ዛሬ ከተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ማጠናቀቂያ በኋላ፣ በምክር ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ጠ/ ሚዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ላለፉት 5 ዓመታት በፓርላማው መድረክ የሕዝብን ድምፅ ሲያስተጋቡና የተለያዩ አገራዊ ጥያቄዎችን በንቃት ሲያቀርቡ የቆዩ ተሰናባች ተቃዋሚ የምክር ቤት አባላት ተሳትፈዋል።
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት 2.34 ትሪሊየን ብር ሆኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።
የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይህ በጀት የአገሪቱን የፋይናንስ አቅምና የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲን ያገናዘበ መሆኑን በውሳኔ ሃሳቡ አመልክቷል።
ከተያዘው አጠቃላይ ወጪ ውስጥ 1.49 ትሪሊየን ብር ከታክስ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አሳውቋል።
ይህን ግብ ለመምታት የታክስ አስተዳደርን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋትና የታክስ ፖሊሲ ክፍተቶችን ማሻሻል ወሳኝ መሆኑን አስረድቷል።
የክልል መንግስታት የበጀት ድጋፍን በተመለከተ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባጸደቀው የድጎማ ቀመር መሠረት የተደለደለ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አመልክቷል።
በጀቱ በበጀት መሸፈኛ ራስን የመቻል አቅጣጫን የተከተለና የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጿል።
በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሕግና ደንብን የመጣስ አዝማሚያ በተደጋጋሚ እንደሚታይ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዋና ኦዲተርን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ገልጿል።
ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ በቁጠባና በላቀ ውጤታማነት እንዲጠቀሙና ከሥርዓት ውጭ ለሚደረግ የበጀት አጠቃቀም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስቧል።
በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ለተጨማሪ ወጪና ለመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል።
በተለይ በመንገድ ግንባታ ምክንያት መሬታቸውን ለለቀቁ ዜጎች የሚገባቸው የካሳ ክፍያ በሕግ በተደነገገው ጊዜና መጠን በአፋጣኝ እንዲፈጸም የሚመለከታቸው ተቋማት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ በውሳኔ ሃሳቡ አሳስቧል።
ከውሳኔ ሃሳቡ በኋላ ምክር ቤቱ በጀቱን በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" የምታውቀውን፣ ያየኸውን፣ የመንግስትም ጥፋት ከሆነ ግለጥ፤ ችግር የለውም። የማታውቀውን፣ ያልነበርክበትን ቦታ እስላም ነው፣ ክርስቲያን ነው፣ አማራ ነው፣ ኦሮሞ ነው እያልክ የቡድን ጨዋታ መጫወት ግን አስፈላጊ አይደለም " - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምን አሉ ?
" በአለም ላይ አጠቃላይ ያለው ግጭት አራት መንስኤ አለው። አብዛኛው ግጭት መንስኤው ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ሪዮተ አለም ነው። ሁለተኛው የኢኮኖሚ የበላይነት ነው። ሶስተኛው፣ የበላይነት ለማስፈን ፤ አንደኛ ዜጋ ለመሆን ነው። አራተኛው፣ ግዛት ማስፋፋት ነው።
እነዚህ ግጭቶች ግን አብዛኛው የሚደበቁት ሃይማኖት እና ብሄር ውስጥ ነው። ' ግዛት ላስፋፋ ነው ' የሚል የለም፣ ' የኢኮኖሚ የበላይነት ልቆጣጠር ነው ' የሚል የለም፣ ይህን ፍላጎት ደብቆ በሃይማኖት እና በብሄር ጥላ ስር ግጭት ይፈጠራል።
ሃይማኖትን ለግጭት የሚጠቀሙ ሃይሎች አሉ፣ ሃይማኖቶቹ ግን እስላምም ክርስቲያኖቹም አጠቃላይ ሁሉም የሰላም እምነቶች እንጂ የግጭት እምነቶች አይደሉም። ለዚህ ማረጋገጫው ኢትዮጵያ ናት።
ለረዥም አመታት ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቂት ክርስቲያኖች ካሉ፣ ሙስሊሞች አዋጥተው፣ አግዘው ቤተክርስቲያን ይሰራሉ። በእኛ ሃገር የምናውቀው እሱን ነው። ብዙ ክርስቲያን ባለበት፣ ጥቂት ኢስላም ባለበት ክርስቲያኖች አግዘው፣ ደግፈው መስጊድ ይሰራሉ። አብዛኛው ታሪካችን ይሄ ነው።
በቅርቡ ጥናት አጥንተን ነበር። ከግማሽ በላይ ከ50% በላይ የሙስሊም ማህበረሰብ ያለባቸው ወረዳዎች አብዛኛው ሙስሊም የሆነበት ወረዳዎች 1,263 ቤተክርስቲያኖች አሉ፤ አብዛኛው እስላም የሆነበት አካባቢ። ከ1 ሺህ ውስጥ ስንት ቦታ ነው ግንጭት የምንሰማው ነው አሁን ? የሃይማኖት ግጭት ካለ አብዛኛው ሙስሊም ያለበት አካባቢ ሁሉም ቦታ ግጭት ይጠበቅ ነበር። ግን የእስልምና ባህሪ ግጭት አይደለም። የክርስትና ባህሪ ግጭት አይደለም።
ክርስቲያኖች የበዙባቸው አካባቢዎችም እንደዚሁ መስጂዶች አሉ የምንሰማው ችግር ግን ጥቂት ቦታ ነው። በዚህ ሁሉ ስፋት ችግር አንሰማም።
አስተውላችሁ ከሆነ ነውጠኞች ክብሪት ፣ ጭድ ይዘው ይለኩሳሉ። ጀሌዎቻቸው እዚሁ አዲስ አበባ ተቀምጠው ቤንዚን እያርከፈከፉ እሳቱን ያራግቡታል። ለኳሽ እና አራጋቢ ማዶ ለማዶ ተቀምጠው ችግሩን የእምነት ፣ የብሄር መልክ ለመስጠ ይሞክራሉ።
የአርሲን ግጭት እውሰድ ፤ የአርሲ ግጭትና የአንዳንድ ሰዎች የኮሙኒኬሽን ዘዴ አሳፋሪ ነው።
የምርጫ ጣቢዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለነበር (ጥቃት እንዳይደርስ) ወደ አርሲ ሄዱ (በተለያዩ ከተሞች ጥቃት ለማድረስ ሞክረው ያቃታቸው ኃይሎች)።
እዛ መንደር ህዝብ የሚከላከል ኃይልና ህዝብ የሚያጠቃ ኃይል ተጋጠመ።
በጥቅሉ አርሲ በነበረው ግጭት ህይወታቸው ያለፈ 11 ሰዎች ናቸው። ከ11ዱ ሰዎች ስምንቱ ሚሊሻ እና ፖሊስ ናቸው፣ ህዝባቸው እንዳይገደል ተፋልመው፣ ህይወታቸውን ገብረው የብዙ ንጹሃን ዜጎችን ህይወት የታደጉ ናቸው። እነዚህ ፖሊስና ሚሻዎች ክብር አይገባቸውም ? ቤተሰብ፣ ልጆች የላቸውም ? ለኛ ሞተው ሲያበቁ እነሱን እንደማወደስ የነሱን መስእዋትነት ማራከስ በብዙ ፖለቲከኞች ይታይ ነበር። አሳፋሪ ነው !
በእርግጥ 3 ንፁሃን ዜጎች ሞተዋል።
ግጭቱን የሃይማኖት መልክ ለመስጠት ታስቦ ነበር። ግን እዚህ ውስጥ ሙስሊሞች ሞተዋል።
በነገራችን ላይ ሙስሊሞች የሞቱት በንጹሃን ዜጎች በኩል ብቻ አይደለም። ህዝብ ለመታደግ እየተፋለሙ የሞቱ ሚሊሻ እና ፖሊሶች ሙስሊሞች ያሉበት ነው።
ምኑ ነው የሃይማኖት ግጭት ? ሰው እንዳይመታ እየተዋደቀ ያለን ሰው በሃይማኖት ጥላ መውቀስ ተገቢ ነው ወይ ? ነገሩን በወጉ በቅጡ ሳይገነዘቡ ማራገብ ተገቢ ነው ? ይሄ አይጠቅመንም። ከዚህ የሚገኝ ፖለቲካዊ ትርፍም አያዋጣም። የሞተው ወንድማማች ነው።
ውጊያው የእምነት ሳይሆን ሽፍቶች ሰው ገድለው፣ ሰው አፈናቅለው የነበረውን ሰላማዊ ድባብ ለማጠልሸት ስራ ተሰጥቷቸው ነው። ግን ድርጊቱ እዛ ብቻ እኮ አይደለም በርካታ ቦታ ነበር የታቀደው። ሌላውን አክሽፈነው ነው።
በዚያ ቦታ ላይ ህዝባቸውን ለመታደግ መስዋትነት ለከፈሉ የፖሊስ እና ሚሊሻ አባላት የተከበረው ምክር ቤት ክብር እንዲሰጥልኝ በትዕትና እጠይቃለሁ።
በጉዳዩ የተሳተፉ 22 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ። በርካታ ያባባሱ ሰዎችም ተይዘዋል። ከተፈናቀሉት ዜጎች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል። የቀሩትም በቅርቡ ይመለሳሉ። በነበረው ግጭት ሸሽተው የወጡ ሰዎች ነበሩ፤ እነሱ ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ።
በዚህ አጋጣሚ ማስጠንቀቅም አደራ ማለትም የምፈልገው፣ አዲስ አበባ ተቀምጣችሁ ጫት እየቃማችሁ በሌላችሁበት ቦታ በሶሻል ሚዲያ የምታራግቡ ሰዎች ጥንቃቄ አድርጉ። እዚህ ሆኖ ባላጣራው ጉዳይ የሚያራግብ ሰውንና እዚያ የሚጋጨውን ሰው ለይተን አናይም።
የምታውቀውን፣ ያየኸውን፣ የመንግስትም ጥፋት ከሆነ ግለጥ፤ ችግር የለውም። የማታውቀውን፣ ያልነበርክበትን ቦታ እስላም ነው፣ ክርስቲያን ነው፣ አማራ ነው፣ ኦሮሞ ነው እያልክ የቡድን ጨዋታ መጫወት ግን አስፈላጊ አይደለም። በጥቅሉ ስለሚጎዳን ጥንቃቄ ብታደርጉ ጥሩ ነው ፤ አጋጣሚ ሆኖ ስለተመረጥን " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia
" የቤት ኪራይ ከአብዛኛው ዜጎቻችን ወርሃዊ ገቢ በላይ ሆኗል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን መካከለኛ የሚባል የህብረተሰብ መደብ ጠፍቶ ጥቂት እጅግ የበለፀጉ እና አብዛኛው በድህነት የሚማቅቅ ሁለት መደቦች ሆነዋል " - ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)
የፓርላማ አባሉ ደሳለኝ ጫኔ(ዶ/ር) ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል።
ደሳለኝ (ዶ/ር) "ላለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ የከፈለው ዋጋ እጅግ የበዛ እና ከባድ ነው እርሶ ስልጣን ላይ ሲቀመጡ የገቡት የሰላም እና የብልጽግና ቃልኪዳን ነበር በተግባር ያየነው ተገላቢጦሹን ነው" በማለት ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል።
"የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያስከተለው አስከፊ ሰብአዊ ውድመት እና ጠባሳ ሳይሽር ዛሬም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በሌሎችም አካባቢዎች የሚታዩት ቀጣይነት ያላቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች፣ ብሄር እና ሀይማኖት ተኮር ጥቃቶች፣ እገታዎች እና አለመረጋጋቶች የዜጎችን የመኖር መብት ነፍገዋል" ሲሉም አክለዋል።
በቅርቡም "ከትግራይ እና ከኤርትራ ሀይሎች ጋር የሌላ ጦርነት ስጋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል" ሲሉም ጉዳዩ የደረሰበትን አሳሳቢነት ጠቁመዋል።
በዝርዝር ባቀረቡት ጥያቄ ምን አሉ ?
" በፖለቲካው መስክ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ፣ የሀገራዊ ተቃርኖዎች መስፋት ወይም Political Polarization፣ የሲቪክ ማህበራት መኮስመን፣ በጋዜጠኞች እና በሚዲያዎች ላይ እገዳዎች እና ክልከላዎች ዜጎች አማራጭ ድምፅ እንዳያሰሙ አፍነዋቸዋል።
በርካታ የፖለቲካ እስረኞችም ህገ-መንግስታዊ የፍትህ ዋስትና ተነፍገው ይገኛሉ። ይህ አጠቃላይ የሰላም፣ የፀጥታ እና የፖለቲካ ውድቀት የፓርቲዎ የተሳሳተ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ውጤት፣ አንድነትን በተግባር ማምጣት ያቃተው የመደመር ትረካ መዋቅራዊ ስብራት ውጤት ነው።
መንግስት የችግሮቹን ስር መሰረት ትቶ ምልክቶቹን ብቻ የመቀጥቀጥና እና በቁጥር ጨዋታ ህዝብን የማደናገር አካሄድ እየተከተለ ነው።
በተላከልን የመንግስት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በ2018 በጀት አመት 10.2% እንደሚያድግ፣ የግብር ገቢ 1.5 ትሪሊዮን ብር መድረሱ፣ የሸቀጦች ወጪ ንግድ 11 ቢሊዮን ዶላር ማስገኘቱ እና የውጭ ቀጥታ ሃዋላ ፍሰት ኢንቨስትመንት 7.7 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተገልጿል።
ነገር ግን እነዚህ የቁጥር ስኬቶች የዜጎችን የመኖር እውነታ ፍፁም አይወክሉም፤ እንዲያውም መሬት ካለው እውነታ ጋር በፅኑ ይጋጫሉ። ምክንያቱም የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት ከገቢያችን ጋር አልተመጣጠነም።
ሪፖርቱ እስከ ግንቦት 2018 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 13.4፣ የምግብ የዋጋ ግሽበት ደግሞ 15% ደርሷል ይላል።
ይህን ግሽበት ለመደጎም መንግስት 379 ቢሊዮን ብር ማውጣቱ ቢገለፅም በተግባር ግን ባለፉት አመታት የተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዝቅተኛውን የማህበረሰብ ክፍል ለከፋ ድህነት በዳረገበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን።
ማሻሻያውን ተከትሎ የመጣው ሰማይ የነካ የዋጋ ግሽበት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የመግዛት አቅም ሙሉ በሙሉ አሳጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ ቋሚ ደሞዝ የሚከፈላቸው የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ሰራተኞች፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች፣ አነስተኛ ነጋዴዎች፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ወገኖቻችን በስውር ረሀብ ውስጥ ወድቀዋል።
የቤት ኪራይ ከአብዛኛው ዜጎቻችን ወርሃዊ ገቢ በላይ ሆኗል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን መካከለኛ የሚባል የህብረተሰብ መደብ ጠፍቶ ጥቂት እጅግ የበለፀጉ እና አብዛኛው በድህነት የሚማቅቅ ሁለት መደቦች ሆነዋል።
በሪፖርቱ መረጃ መንግስት በበጀት አመቱ 1.13 ትሪሊዮን ብር ብድር መልቀቁን እና 91% የሚሆነው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ ነው ይላል።
ክቡር የብሄራዊ ባንክ ገዢ እና የፋይናንስ ሚኒስትርም በተደጋጋሚ ላለፉት አመታት መንግስት አንድም ሳንቲም የንግድ ብድር (Commercial Loan) አልተበደረም እያሉ ይናገራሉ።
ይህ የውጭ ንግድ ብድርን ብቻ ነጥሎ በማየት እውነታውን የማደብዘዝ አካሄድ ነው። መንግስትዎ በግምጃ ቤት ሰነድ እና በሀገር ውስጥ እዳ ዋስትናዎች አማካኝነት ከሀገር ውስጥ ባንኮች እና ተቋማት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር እየተበደረ መሆኑን እና ይህም የሀገር ውስጥ እዳ ሸክምን በከፍተኛ ደረጃ እንዳንናረው እና የግሉ ዘርፍ ብድር እንዳጠበበው ለምን ተደበቀ?
በየጊዜው በዚህ ፓርላማ የምናፀድቃቸው በቢሊዮኖች ዶላሮች የሚቆጠሩ የእርዳታ ብድሮች (Concessional Loans) ለምን በሪፖርቱ አይካተቱም? የእዳ ምንጭ እና አይነት መለወጡ እዳ መኖሩን ያስቀራል ወይ?
ሪፖርቱ አሁንም ድረስ ከዩሮ ቦንድ ባለቤቶች ጋር ያለው ድርድር ስላልተጠናቀቀ ሀገሪቱ በከፍተኛ የእዳ ቀውስ ውስጥ ያለች ወይም Debt Distress መሆኗን ይሸሽጋል።
ሌላው የትምህርት እና የማህበራዊ ዘርፍ መውደቅ አለ በሪፖርቱ ላይ 26 ሚሊዮን ተማሪዎች በመመዝገባቸው በስፋት ቢወራም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 50% እና ከዚያ በላይ ማምጣት የቻሉት 8.7% ወይም 50 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ናቸው።
ይህም የመንግስትዎ የትምህርት ጥራት መዋቅራዊ ኪሳራ የሚያሳየን ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከ8.7% የማለፍ ምጣኔ በየትኛውም አለም ታይቶ የማይታወቅ ወይም 92% የመውደቅ ምጣኔ ከፍተኛ የትውልድ ብክነት ወይም Generational Catastrophe ነው።
እኔ የህይወቴን ግማሽ ጊዜ በማስተማር ያሳለፍኩበት በተለያዩ ደረጃዎች እና ኮመን የሚባል አባባል አለ፤ 'መምህሩ ፈተና አውጥቶ ተማሪዎችን ማሳለፍ ካልቻለ እና ከወደቁ የወደቀው መምህሩ ነው' የሚል ኮመን አባባል አለ በእኛ በአስተማሪዎች ዘንድ። እና ይህን ያህል 92% የመውደቅ ምጣኔ ካለ እኔ ወደቋል ብዬ የማስበው ትምህርት ሚኒስቴር ነው።
በዚህ ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ ሂደት ውስጥ አልፈው ለምረቃ የበቁ ወጣቶችም የስራ እድል የላቸውም ይባስ ብሎም ወደ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ተማሪዎች አሁንም ድረስ ከትምህርት ገበታቸው ተገልለው ይገኛሉ። ይህ 7 ሚሊዮን አሃዝ ከ20 በላይ የአፍሪካ ሀገራት እያንዳንዳቸው ካላቸው አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር በላይ መሆኑንም ልብ ይሏል።
ሌላው የሰብአዊ ቀውሶች ትኩረት አለመስጠቱ ነው መንግስትዎ የመረጃ ማጥራት ስራ ሰርቻለሁ በሚል ሰበብ የሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር ከ27 ሚሊዮን ወደ 2.3 ሚሊዮን ወርዷል ይላል።
ነገር ግን መሬት ላይ በጦርነት እና በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ፣ የለጋሾች እርዳታ ያጡ፣ ለቤተሰቦቻቸው ፍጆታ በቂ ምርት የማይያመርቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እያሉ ይህንን ቁጥር ወደ 2.3 ሚሊዮን ዝቅ አድርጎ ማቅረብ ፖለቲካዊ የቁጥር ማሳመር እንጂ የዜጎችን ነባራዊ ህይወት በተጨባጭ የሚያሳይ አይመስለኝም።
እነ WFP፣ FAO፣ Famine Early Warning Network የሚያስቀምጡት ዝቅተኛ ግምት ከ15.8 እስከ 21.4 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የምግብ እጥረት ውስጥ እንደሚገኙ ነው " ብለዋል።
ምን የመፍትሄ ሃሳብ አቀረቡ ? ያንብቡ👇 https://www.facebook.com/share/p/18qeyGGbhG/
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia