#AddisAbaba
የትራፊክ ማኔጅመንት የራሱን የተቋሙን በከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኙ ኀላፊን ማብራሪያ " የእኔ አቋም አይደለም " አለ።
በአዲስ አበባ ከተማ የኮድ 2 ተሸከርካሪዎች በፈረቃ እዲንቀሳቀሱ ሊደረግ መሆኑን ይህም ከ2 እስከ 3 ወር ባለው ጊዜ ወደ ተግባር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ማሳወቁ ይታወቃል።
መ/ቤቱ ይህንን ያሳወቀው በአንድ ከፍተኛ አመራሩ ነው።
በዛሬው ዕለት ደግሞ እራሱ ባለስልጣን መ/ቤቱ " ይሄ ወደፊት በጥናት የሚሆን እንጂ በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆን አይደለም " ብሏል።
መ/ቤቱ ፤ " ' በአዲስ አበባ ከተማ ጥዋት እና ማታ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ኮድ 2 ተሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ ሊደረግ ነው ' በሚል ርእስ በተቋሙ የትራንስፖርት ቁጥጥር ደንብ ማስከበር ኩነት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር /ተወካይ/ አቶ አያሌው ኢቲሳ ለሸገር ኤፍ ኤም የሰጡት ማብራሪያ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አቋም አይደለም " ብሏል።
" ግለሰቡ ' ጎዶሎ ቁጥር እና ሙሉ ቁጥር የኮድ 2 ተሽከርካሪዎችን በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱንና የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን፥ በሁለት እና በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ በከተማው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኮድ 2 ተሽከርካሪዎች ወደ ፈረቃ እንዲገቡ ይደረጋል ' ያሉት ከተቋሙ ያገኙትን መረጃ ተንተርሰው አይደለም " ሲል አክሏል።
"ጎዶሎ ቁጥርና ሙሉ ቁጥር ኮድ 2 ተሽከርካሪዎችን በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ ወደ ፊት ከመንግስት በሚሰጥ አቅጣጫ ተጠንቶ የሚሆን እንጂ በአሁኑ ወቅት ይህንኑ ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ የለም " ብሏል።
በአዲስ አበባ የኮድ 2 ተሽከርካሪዎች ከ2 እስከ 3 ወር ባለው ጊዜ በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ ሊደረግ መሆኑን ያሳወቁት የአ/አ ትራፊክ ማኔጅመንት ፦
- የትራንስፖርት ቁጥጥር ደንብ/ማስ/ኩነት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር
- የተቋሙ ተወካይ
- በተቋሙ ውስጥ የሚሰሩ
- የህግ ማዕቀፍም ተዘጋጅቶ ማለቁን በእርግጠኝነት የተናገሩ ሰው ናቸው።
ነገር ግን ይህ መረጃ ይፋ ከሆነ ከአንድ ቀን በኋላ ተቋሙ " የግለሰቡ ማብራሪያ እኛን አይወክልም ፤ ማብራሪያውን የሰጡት ከተቋሙ መረጃ አግኘትውም አይደለም " ብሏል።
ይህን ማስተባበያ የተመለከቱ አስተያየት ሰጪዎች ቀድሞውኑ የህዝቡ ትርታ ለማድመጥ የተደረገ ነው ብለውታል።
" እንዴት አንድ ተቋም የራሱን ሰራተኛና ከፍ ባለ ቦታ የሚገኝ ኃላፊ እኔን አይወክልም ይላል ? " ሲሉ ጠይቀዋል።
በመሰረቱ ይህ ተግባራዊ ይደረግ ቢባልም የማይሆን እንደሆነ አስምረውበታል።
#AddisAbaba #ኮድ2
#EDR
ኢጂነር ታከለ ኡማ ሹመት ተሰጣቸው።
ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢንጂነር ታከለ ኡማን ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር አ.ማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አድርገው እንደሾሟቸው የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር አ.ማ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አሳውቋል።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ ላለፉት ዓመታት በትምህርት ላይ ነበሩ።
ለትምህርታቸው ወደ ውጭ ሀገር ከመጓዛቸው በፊት የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ከዛ ቀድሞ አዲስ አበባ አስተዳደርን በከንቲባነት ሲያገለግሉ እንደቆዩ ይታወሳል።
" በታሪኬ ከታክስ በፊት ከፍተኛውን ትርፍ አግኝቻለሁ " - ንግድ ባንክ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት 135.4 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን አሳውቋል።
በዚህ ዓመት ከታክስ በፊት የተገኘው 25.6 ቢሊዮን ብር ትርፍ እንደሆነ እና በባንኩ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን ገልጿል።
የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1.17 ትሪሊዮን ብር የተሻገረ መሆኑን ተናግሯል።
የባንኩ የደንበኞች ቁጥር ደግሞ ከ45 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ አመልክቷል።
የተበላሸ ብድር ክምችቱ 2.6% መደረሱም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፥ ከ218 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ማቅረቡን ጎልጾ 91% ወይም ብር 198 ቢሊዮን የሚበልጠው ለግሉ ሴክተር የተለቀቀ ብድር እንደሆነ አሳውቋል።
" የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ወታደር ዜጎችን በጅምላ አይገድልም " - ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ሀገር መከላከያ ሰራዊት በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱን በወታደራዊ ፍርድ ቤት ስርዓት እስር ቤት እንደሚገቡ ማድረጉን ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
ዶ/ር ዐቢይ ፤ መከላከያ ከ ' Code of conduct ' ውጭ በማይገባ መንገድ ኦፕሬሽን ሰርታችኋል በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱን እስር ቤት እንዳስገባ አሳውቀዋል።
የጅምላ ግድያን በተመለከተ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ " የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ወታደር ዜጎችን በጅምላ አይገድልም " ሲሉ ተናግረዋል።
" በጅምላ ለማሸነፍ ይነሳና ሲሞት ነው በጅምላ ሞትኩኝ የሚለው እንጂ መንግሥት አይገድልም " ሲሉ ገልጸዋል።
" ማንኛውም ስህተት በፈተጠረበት ደግሞ ኃላፊነት ወስደን እናርማለን " ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ " እንዴት አድርገን ህዝባችንን እንገድላለን ? ማነው እራሱን የሚገድለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማለት ሁሉም ነው " ብለዋል።
ያም ቢሆን ግን ለተፈጠሩ ስህተቶች ፣ በየቦታው ለሚያጋጥሙ ስህተቶች ግለሰብም ቢሆን ችግር ከፈጠረ ይጠየቃል ሲሉ ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊቱ ስርዓት ያለው ቢሆንም በግለሰብ ደረጃ ችግር የፈጠረ ይጠየቃታል ሲሉ አክለዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምን ጠየቁ ?
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አበባው ደሳለው ፦
" የመንግስት ኃላፊዎች በተለያየ ጊዜያት በተደጋጋሚ ስለ ሀገራዊ ምክክር እና ስለ ሽግግር ፍትህ ሲያነሱ ይደመጣል።
ነገር ግን ከሀገራዊ ምክክር እና ከሽግግር ፍትህ በፊት መቅደም ያለባቸው ነገሮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንደኛውና ዋነኛው የእምነት ግንባታ ነው።
መንግስት በህዝብ ዘንድ እምነት አልገነባም ብለን እናስባለን። ይሄም የሚገናኘው ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ነው።
ባለፉት 10 ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሰበብ በማድረግ የመንግስት ኃይሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል።
ከነዚህ ጥሰቶች ውስጥ የጅምላ ግድያ፣ በሰብዓዊ / ባልታጠቁ ዜጎች ላይ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል። በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች።
ጥቂቱን ለመጥቀስ በመርዓዊ ፣ በጅጋ ፣ በደብረ ኤልያስ ፣ በፍትኖተ ሰላም፣ ደብረሲና አካባቢ ፣ ጎንደር እና ወሎም እንዲሁ ተፈጽሟል።
ይህንንም የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተቋማት የዘገቡት የአይን እማኞችም የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው።
ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጾታዊ ጥቃት፣ ድብደባ ፣ ዘረፋ ፣ ንብረት ማውደም ፣ የሲቪል ተቋማት በጤና ፣ በትምህርት ተቋማት ላይ ውድመት እንደደረሰ በርካታ ምስክሮች ገልጸዋል።
ሌላው የሰብዓዊ መብት ችግር በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት በርካታ ፖለቲከኞች የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ታስረዋል።
ከዚህ ባለፈ ጋዜጠኞች፣ አንቂዎች፣ አጠቃላይ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በተለይ በአማራ ክልል አማራዎች በጅምላ ለወራት በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ።
የምክር ቤት አባላትን ስናነሳ የምክር ቤት አባላችን አቶ ክርስቲያን ታደለ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኖ መንግስትን ከምዝበራ ያዳነ በሰላማዊ ትግልም በእጅጉ የሚያምን ሰው ነው አንድ አመት ለሚሞላ ጊዜ በእስር እየማቀቀ ያለው።
ሌሎችም በለውጡ ከእርሶ ጋር አብረው የሰሩ እንደ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ፣ ዶ/ር ካሳው ተሻገርና አቶ ታዬ ደንደአ ያሉም ለውጡ ስህተት ፈጽሟል በትክክለኛው ጎዳና እየሄደ አይደለም ብለው ስለሞገቱ ብቻ ለወራት ታስረዋል።
ከዚህ የከፋው ግን የት እንኳን እንደታሰረ የማይታወቅ አንድ የአብን አባላችን ነው ሀብታሙ በላይነህ ይባላል።
ሀብታሙ በላይነህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ነው። እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ መምህር ነው። ላለፉት 4 ወራት የት እንደገባ አይታወቅም። ይህን ጉዳይ ቤተሰቡም እኔም ለተለያየ የመንግስት ኃላፊዎች አቤት ብለናል ምላሽ አላገኘንም። ዛሬ እርሶ ምላሽ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ እንማጸናለን።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ልክ እንዳበቃ ህጋዊ አሰራሩ ይቀጥላል ብለን እንገምት ነበር ነገር ግን አዋጁ አብቅቶ በኮማንድ ፖስቱ እየተዳደርን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
የጅምላ እስር አሁንም አለ፣ ህገመንግስቱ በትክክል እየሰራ አይደለም። በደረቅ ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ብቻ መጠየቅ ሲገባቸው አሁንም በፖለቲካ አመለካከታቸው ዜጎች በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ።
ስለዚህ ህብረተሰቡ ስለ ሽግግር ፍትህና ስለ ሀገራዊ ምክክር መንግስት ሲያወራ ይመነው ? እምነት አልገነባንም።
በጅምላ የታሰሩ፣ የህሊና እስረኞች ቢፈቱ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መርምረው አጥፊዎች ተጠያቂ እዲሆኑ ቢደረግ ያኔ እምነት መገንባት ይቻላል።
መንግስት ምን እቅድ አለው እምነት ለመገንባት ? የህሊና እስረኞችን ለመፍታት እና የጅምላ ግድያና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማቆም ምን ወስኗል ? "
የምክር ቤት አባላት ምን ጠየቁ ?
" አጠቃላይ የሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች በዋና ዋና አመላካቾች በምን ደረጃ ላይ ናቸው ?
በተለይ የኑሮ ውድነት እየከፋ ነው።
የዋጋ ንረትን ደግሞ ማረጋጋት አልተቻለም።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ማህበረሰብ እና የመንግሥት ሰራተኛው መኖር አቅቶታል።
መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው።
ስለሆነም እንደ መንግሥት በቀጣይ አመታት እነዚህን ተግዳሮቶች ለመወጣትና የህዝቡን ጥያቄ ለመፍታት በምን ደረጃ ታቅዷል። "
(አቶ አቤነዘር በቀለ - የተ/ም/ቤት አባል)
#HoPR
ዛሬ የህዝብ ተወካዮች ም/ ቤት 36ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ተገኝተዋል።
በስብሰባው የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
በአሁን ሰዓት የምክር ቤት አባላት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው።
#Update
የሀገር መከላከያው ስለ ትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ የማድረግ እንቅስቃሴ ምን አለ ?
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጄነራል ብርሃኑ በቀለ ከብሄራዊ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።
የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነትን መሰረት በማድረግ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሀገር መከላከያው ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ እንዲያስተባብር አቅጣጫ ተሰጥቶ እየሰራ እንዳለ አመልክተዋል።
የፀለምት እና አካባቢው ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው የመመለስ ስራ ኃላፊነት የተሰጠው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ መሆኑን ተናግረው " ስራው እጅግ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው " ብለዋል።
ዛሬን ረቡዕ ጨምሮ ባለፉት ቀናት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቄያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሌ/ጄነራሉ ፥ ተፈናቃዮች እየተመለሱ ያሉት አስፈላጊና መሟላት አለባቸው የተባሉ ቅድመ ሁኔታዎች ከጎን እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ስራው በፍጥነት እየሄደ ያለው አብዛኛዎቹ አርሶ አደር የክረምቱ ወቅት ሳያልፍ እርሻውን እንዲሰራና ህይወቱን እንዲመራ በማሰብ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በፀለምት ካሉ 25 ቀበሌዎች አብዛኛው ተፈናቃይ ከ22 ቀበሌዎች ነው አሁን ባለው ሁኔታ በአስራዎቹ ቀበሌዎች ተፈናቃይ ተመልሷል ፤ እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ቀሪ 11 ቀበሌዎች አብዛኛው እንዲገባ ይደረጋል ሲሉ አሳውቀዋል።
የቀረውም ስራ በቀጣይ ይሄዳል ብለዋል።
ስለ ታጣቂዎች መውጣት ምን አሉ ?
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ " የትግራይ ታጣቂዎች በኃይል ገብተዋል " ስለሚባለው ጉዳይ ሌ/ጄነራሉ ፥" ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኃላ በፀለምትም ይሁን በወልቃይት በኃይል የገባባቸው ቦታዎች የሉም " ሲሉ መልሰዋል።
ፀለምት ካሉት ቀበሌዎች 3 ቀበሌዎች ላይ የትግራይ ታጣቂዎች እንዳሉ እነዚህም ጦርነት ሲቆም ባሉበት የቆሙ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል።
ባለው መግባባት ከሁለቱም ክልል ጋር የሁለቱም ክልል ታጣቂ መውጣት ስላለበት ተፈናቃዮችን በመመለስ ታጣቂዎቹን የማስወጣት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ፀለምት ያለው የትግራይ ታጣቂ እንዲወጣ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከተፈናቃይ ጋር ታጣቂ እንዳይመለስ ስለሚሰራ ስራ ምን አሉ ?
በአማራ በኩል " ከተፈናቃይ ጋር ታጣቂ ይገባል " የሚል ስጋት እንዳለ ያልሸሸጉት አዛዡ ፥ በትግራይ በኩልም " ታጣቂዎች (በአማራ በኩል ያሉ) እንደ አዲስ ተደራጅተዋል ስጋት ናቸው " የሚል ነገር እንዳለ ገልጸዋል።
" የሀገር መከላከያው ከሁለቱም በኩል ከተፈናቃዮች እና እዛው ከነበሩት ነዋሪዎች ( ካልተፈናቀሉት ) ሽማግሌዎች እንዲውጣጡ አድርጎ የተፈናቃዮችን ዝርዝር ለመከላከያ ተሰጥቶ ከዛም መከላከያው ከሽማግሌዎቹ ጋር አብሮ ሰዎቹ የዛ ቦታ ነዋሪ መሆናቸውን እየጠየቀና እያረጋገጠ ተፈናቃዮች ይመለሳሉ " ብለዋል።
' ይሄ ታጣቂ ነው ፣ ይሄ ሚሊሻ ነው ' የሚል ክርክር በሽማግሌ ደረጃ ከተነሳ ወደ ህዝብ ተወስዶ ህዝቡ እራሱ ይፈርዳል ሲሉ ተናግረዋል።
" እንግዳ ሰው ሲገባ ይታወቃል ይህ ጉዳይ አሳሳቢ አይደለም " ያሉት አዛዡ ፥ ገጠር ይሁን ከተማ መሬት ከሌላቸው / ሊገቡበት የሚችሉበት ቤት ከሌላቸው ተለይቶ ይታወቃል ብለዋል።
#Ethiopia
#FDREDefenseForce
@tikvahethiopia
#Sidama
በሀዋሳ ከተማ 1 ሊትር ቤንዚን በድብቅ እስከ 180 ብር እየተሸጠ ነው።
በከተማይቱ ያሉ ሁሉም ማደያዎች ውስጥ ቤንዚን የለም ተብሏል።
ይህን ተከትሎ 1 ሊትር ቤንንዚን ከ150 ብር እስከ 180 ብር በድብቅ እየተሸጠ ይገኛል።
ቀድሞውም ቢሆን በከተማዋ በድብቅ ነዳጅ ይሸጥ ነበር። ዋጋውም 100 ብር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በመላ ከተማይቱ ነዳጅ መጥፋቱን ተከትሎ እስከ 180 ብር ደርሷል።
የከተማ ውስጥ ታክሲዎች በተለይ በከተሞች ዳርቻ ዋጋቸዉን እጥፍ ከማድረግ በዘለለ ኮንትራት ካልሆነ አንጭንም እያሉ መሆኑን ሰምተናል።
አንድ የሀዋሳ ከተማ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል " ዛሬ በሀዋሳ 1 ሊትር ቤንዚል ከ170 ብር ጀምሮ እየተሸጠ ነው። በየትኛውም ነዳጅ ማደያ ዛሬ ቤንዚል የለም " ብሏል።
" አንዳንድ ታክሲዎች ዝም ብለን ከምንቀመጥ ብለው 2 ሊትር ከ320 ብር ጀምሮ እየገዙ ፤ የ5 ብር መንገዶችን በ10 ብር እየጫኑ ነው ፤ ከዛ ውጭ ሌሎች በተለይ ባጃጆች በየጥሻው ቆመው ነው ያሉት " ብለዋል።
የከተማው ትራንስፖርት ቢሮም ሆነ የነዳጅ ጉዳይ የሚመለከተዉ የሀዋሳ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ትናንት ስብሰባ ላይ እንደነበሩ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለመረዳት ችሏል።
ስብሰባውን ተከትሎ እስካሁን ምንም አዲስ ነገር አልተፈጠረም።
በትላንትናው ዕለት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን የሰጡት የከተማዉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ችሎት " ጉዳዩ አገር አቀፍ ችግር ነው " ብለዋል።
በማደያዎች ነዳጅ አለመኖሩን እና መንገድ የጀመረ የነዳጅ ጫኝ ቦቴ እንደሌለ በመግለጽም ማህበረሰቡ እንዲታገስ ጥሪ አቅርበዋል።
አንጋፋው ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ከ ' አዲስ አድማስ ጋዜጣ ' መሥራች አንዱ እና በዋና አዘጋጅነትም ጋዜጣዋን ተወዳጅ ያደረጋት ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ባደረበት ህመም ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ላይ ድንገት ህይወቱ አልፏል።
ነቢይ ተርጓሚ ፣ ገጣሚ ወግ አዋቂ የጥበብ ሰው ነበር።
#ደራ🚨
" የደራ ወረዳ ነዋሪዎች በሁለት ታጣቂዎች መካከል እየተሰቃዩ ናቸው " - ነዋሪዎች
በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ በታጣቂዎች እየተፈጸመ ባለው ጥቃት አሁንም የዜጎች ህይወት እየጠፋ፣ ነዋሪውም ቄዬውን ለቆ ለመሸሽ እየተገደደ ይገኛል።
አንዴ በፋኖ ታጣቂዎች አንዴ ደግሞ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች መከራቸውን እያዩ እንደሆነ ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በወረዳው በተለይ በ13 ቀበሌዎች ከሁለት ሳምንት ወዲህ ተቀስቅሷል በተባለ የጸጥታ መደፍረስ የሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተሰምቷል።
አንድ የጅሩዳዳ ነዋሪ ፥ አራት አርሶ አደሮች በእርሻ ስራቸው ላይ እያሉ መገደላቸውን ገልጸዋል።
ከወረዳው 44 ቀበሌዎች በ18ቱ የታጣቂዎች እንጂ የመንግሥት መዋቅር እንደሌለ ጠቁመዋል።
ሌላ ነዋሪ ፤ " የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ሲመጣ መኪና አስቁሞ የአማራ ተወላጆችን አግቶ ይወስዳል። የፋኖ ኃይል ደግሞ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ እርምጃ ይወስዳል። የደራ ወረዳ ነዋሪዎች በሁለት ታጣቂዎች መካከል እየተሰቃዩ ናቸው። ነዋሪዎች ሰላም ፍለጋ ቄያቸውን እና ንብረታቸውን ጥለው በኤጄሬ በኩል እያቋረጡ ወደ ፍቼ እየሸሹ ነው። ጓደኛዬ የ15 ቀን አራስ ሚስቱን ይዞ ሸሽቷል። ህዝቡ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ነው። መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት አለበት " ብለዋል።
ሌላኛው ነዋሪ ፤ " እየተሰቃየን ይኸው ሁለት ዓመት አሳልፈናል የመንግስት ዝምታ አልገባንም " ያሉ ሲሆን ከቀናት በፊት በቱቲ ቀበሌ በኩል የፋኖ ኃይል ተኩስ መክፈቱን ጠቁመዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪው አቶ ከፍያለው አዳሬ ፤ በደራ ወረዳ የጸጥታ ችግር መኖሩን አረጋግጠዋል።
" የደራ እና ሂዳቡ አቦቴ ነዋሪዎች ብዙ ጊዜ በፋኖ እና ሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት ይደርስባቸዋል። ታጣቂዎቹ የነዋሪዎችን ቤት ያቃጥላሉ፣ ሰዎችንም ያግታሉ። ሁለቱም ኃይሎች ህዝቡን በብሄር እና በሃይማኖት ለማጋጨት በተደጋጋሚ ይጥራሉ። ለምሳሌ ፦ ' ፋኖ ነኝ ' ባዩ አካል የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ንብረት ያወድማል ፤ የሸኔ ታጣቂም እንደዛው የአማራ ብሄር ተወላጆችን ንብረት ያወድማል " ብለዋል።
" የመንግስት የጸጥታ ኃይል በሁለቱም ታጣቂ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው " ሲሉ አክለዋል።
" ደራ ወረዳ አልፈረሰችም የመንግሥት ማዋቅርም አለ " ያሉት አስተዳዳሪው " የመንግስት ኃይል በማይደርስባቸው ቦታዎች ሰላም ለማስፈን አስቸጋሪ ሆኗል " ብለዋል።
" ታጣቂው ኃይል በእነዛ ቀበሌዎች ነው ያለው ግን ሌላም ቦታ ገብቶ አያጠፋም ማለት አይቻልም ፤ ይህ ታጣቂ ኃይል ከሌላ አካባቢ የመጣ ሳይሆን ከዚሁ አፋና ኦሮሞ እና አማርኛ ተናጋሪ ህብረተሰብ ውስጥ የወጣ ነው ገሚሱ ተገዶ ሌሎቹ ፈቅደው ነው የታጣቂውን ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው ለሰላም ጠንቅ ሆነዋል " ሲሉ አክለዋል።
አቶ ከፍያለው የደራ ጸጥታ ጉዳይ ሰራዊት / የጸጥታ ኃይል በማስለፍ ብቻ መፍትሄ እንደማያገኝ ገልጸው ነዋሪዎች ለሰላም መስራት አለባቸው ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የዚህ መረጃ ባለቤት የቪኦኤ ሬድዮ አማርኛው ክፍል (ጸሐይ ዳምጠው) መሆኑን ይገልጻል።
#AddisAbaba
" በትልቅ ቁጠባ በ33 ቢሊዮን ነው እየተገበረ ያለው " - ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፥ የከተማው 5ቱ ኮሪደር ስራ እየተገበረ ያለው በ33 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህን የተናገሩት ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃል ነው።
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ፥ መጀመሪያ ላይ የ5ቱም ኮሪደር ስራ ሲጠና ኮንሰልታንቶችና አጥኚው ቡድን መንገድ እና የመንገድ መሰረተ ልማት የሚፈጀው ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ እንደገለጹ አስረድተዋል።
" ይህ እንግዴ በወቅቱ ጥናት ነው በዚህ ተለዋዋጭ ገበያ " ያሉት ከንቲባዋ " እስካሁን ድረስ የተጠኑትን 5 ኮሪደሮች እየተገበርን ያለነው በ33 ቢሊዮን ነው " ብለዋል።
በ33 ቢሊዮን ብር እየተተገበረ ያለው ስራም " ትልቅ ቁጠባ የተተገበረበት ነው " ሲሉ ተደምጠዋል።
ስራው ብክነትን በመከላከል፣ የሚወጣውን ወጪም አስፈላጊ ነገር ላይ ብቻ እንዲሆን እየተደረገ ነው ብለዋል።
አንዳንድ በከተማው አስተዳደር የሚሰሩ ስራዎችም ለኮንትራክተሮች እንዳልተሰጡ የተናገሩት ከንቲባዋ ፥ ለአብነት የሜክሲኮ መንገድ በኮንትራክተር ሳይሆን በራስ አቅም መሰራቱን ገልጸዋል።
#Sidama #Hawassa
° " በሀዋሳ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ነዳጅ በመቋረጡ ለከፋ ችግር ተጋልጠናል " - የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች
° " በእጃችን ምንም ነዳጅ ባለመኖሩ ተጠቃሚው ለተወሰነ ጊዜ ይታገሰን " - የሀዋሳ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ
ዛሬ ሰኔ 25 ቀን 2016 በሀዋሳ ከተማ ያሉ ማደያዎች መዘጋታቸውን ተከትሎ በርካታ የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች መቆማቸውን በመግለጽ ቅሬታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
" ከሰሞኑ በሰልፍና በጎን በሚገቡ ህገወጥ ቀጅዎች ስንማረር መሰንበታችን ሳያንስ ዛሬ ደግሞ በየቀኑ በቴሌግራም የሚለቀቀዉ የነዳጅ ፕሮግራም ተቋርጦ በከተማው ውስጥ ያሉ ማደያዎች ሁሉ ዝግ ሆኑብን " የሚሉት አሽከርካሪዎች በዚህም በእጅጉ ተቸግረናል ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የአሽከርካሪዎቹን ቅሬታ ይዞ የሀዋሳ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ችሎትን አነጋግሯል።
እሳቸውም ፤ " እንደከተማ አንድ ማደያ ብቻ አገልግሎት እየሰጠ ነው " በማለት በከተማዉ ምንም አይነት ነዳጅ አለመኖሩን ገልጸውልናል።
የቴሌግራሙ ፕሮግራም አለመውጣቱም ከዚህ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ችግሩ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ስብሰባ መቀመጣቸውን ገልጸው " ማህበረሰቡ እና አሽከርካሪዎች ይህን አውቀው እንዲታገሱ " ሲሉ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ስለ አንካራው ውይይት ምን አለች ?
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአንካራው ውይይት ጉዳይ የፕሬስ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫው በቱርኪዬ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን ጋባዥነት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ ትላንት ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በአንካራ ተገናኝተው መወያየታቸውን አረጋግጧል።
" በቱርኪዬ መንግስት አመቻቺነት የተካሄደው የሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት በሁለቱ አገራት መካከል ላሉ አለመግባባቶች መፍትሄ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ግልፅና ወዳጅነት የተሞላበት የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት ነበር " ብሏል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውን አመልክቷል።
የቱርኪዬ መንግስት ውይይቱን ለማመቻቸት ስለተጫወተው ገንቢ ሚናም ምስጋና እንደቀረበ ገልጿል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠልም እንደተስማሙ አረጋግጧል።
ሁለቱም ሚኒስትሮች የቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ምከከሩን አገራቸው ለማስተናገድ የወሰዱትን ተነሳሽነት በማድነቅ ሁለተኛ ዙር ውይይታቸውን ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በአንካራ ለመቀጠል እንደተስማሙ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቋል።
#Ethiopia🇪🇹
የ12ኛ ክፍል ፈተናን በኦን-ላይን የሚፈተኑ ተማሪዎች ሞዴል ፈተና በአሶሳ ዩኒቨርስቲ እየወሰዱ ነው
የቤኒሻንጉል - ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የ12ኛ ክፍል ፈተናን በኦን-ላይን ለሚፈተኑ ተማሪዎች ሞዴል ፈተና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ሞዴል ፈተናው ለዋናው ፈተና ተማሪዎችን የሚያዘጋጅና ከወዲሁ ተማሪዎቹ እንዲለማመዱ ዝግጁ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ሲሉ በክልሉ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ-ትምህርትና የትምህርት ተቋማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊው አቶ መሀመድ ኡስማን ገልጸዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ሃላፊውና የቢሮው ባለሙያዎችም ተፈታኝ ተማሪዎችን በመዘዋወር የተመለከቷቸው ሲሆን ቀሪ ስራዎችንም ከሚመለከታቸው የዩኒቨርስው ተጠሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም በኦን ላይን ከሚፈተኑ ተማሪዎች መካከል 1,011 የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ሲሆኑ 593 የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ናቸው፡፡
ቢሮው በትስስር ገጹ ላይ ያሳወቀውን የፈተና ድስፕሊን ተማሪዎች እንዲጠብቁና የሚመለከታቸው አካላትም ይህኑ እንዲያስተገብሩ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ መሀመድ ኡስማን አሳስበዋል፡፡
[ዘገባው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ነው]
#Rwanda
በሩዋንዳ በተካሄደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፖል ካጋሜ ከፍተኛ በሆነ ድምጽ የማሸነፍ እድል እንዳላቸው ያልተጠናቀቀ ቆጠራ አሳይቷል።
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን በበርካታ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ላይ ባካሄደው ቆጠራ (79% ቆጠራ) ካጋሜ 99.15 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ይፋ አድርጓል።
24 ዓመታትን ሩዋንዳን በፕሬዜዳንትነት የመሩት ፖል ካጋሜ ውጤቱ ለተጨማሪ 5 ዓመታት በስልጣን እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል።
ሶስት ብርቱ ናቸው የተባሉ ተቀናቃኞቻቸው ከምርጫ ፉክክሩ ውጭ በሆኑበት ነው ምርጫው የተካሄደው።
በምርጫው የተሳተፉት የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋች ፍራንክ ሃቢኔዝ እና ጋዜጠኛና ደራሲ ፊሊፕ ምፓይማና ከ1 በመቶ ያነሰ መራጭ ነው ያገኙት።
ከዚህ በፊት በነበረው የአውሮፓውያኑ 2017 ምርጫ ካጋሜ በ98.8 ድምጽ ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ፖል ካጋሜ እኤአ 1994 የሩዋንዳ የዘር ፍጅት በኋላ በመሪነት ስፍራ የተቀመጡ ሲሆን ከ2000 በኋላም በፕሬዚዳንትነት ቀጥለዋል።
#BBC #AlJazeera
ከሰማይ እንደመጣ የተነገረለት ' ድንጋይ ' ምንድነው ?
በኦሮሚያ ክልል፤ በጅማ ዞን፤ የቡ ከተማ በቅርቡ ከሰማይ እንደመጣ የተነገረለትን ድንጋይ በተመለከተ የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት ማብራሪያ ሰጥቷል።
ማብራሪያ የተሚከተለው ነው ፦
" አስትሮይድ (Asteroid) በህዋ ውስጥ የሚገኙ ድንጋያማ አካላት ናቸው፡፡
በዋነኛነት የስርዓተ ጸሐይ አካል በመሆን በማርስ እና በጁፒተር መካከል ባለው ስፍራ የመቀነት ቅርጽ (Asteroid Belt) ፈጥረው ጸሐይን ይዞራሉ፡፡
እነዚህ የሰማይ አካላት ግዙፍ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹም በመቶ ኪሎሜትሮች የሚቆጠር ዲያሜትር ያላቸው ናቸው፡፡
በአንፃሩ ሜትሮይትስ (Meteorites) ወደ ምድር ከባቢ አየር የገቡ የአስትሮይዶች ወይም ኮሜት ቁርጥራጮች ናቸው።
በሌሊት ሰማይ ላይ የምናያቸው የብርሀን ጅራቶች ሜትሮይድ (Meteoroid)፣ ትንሽ የጠፈር አለት ወደ ከባቢ አየር ውስጥ ሲገባና ሲቃጠል የሚፈጠር ነው።
የሜትዮር ሻወር (Meteor Shower) አስደናቂ የብርሃን ትዕይንት በሰማይ ላይ የሚፈጥሩ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ሜትሮይዶች ጥቃቅን እና መሬት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው የሚጠፉ ናቸው።
በመጠን የገዘፉ እና ጠንካራ የሆኑት አለቶች ከእሳታማው መተላለፊያ እና የመሬት ከባቢ አየር ተርፈው መሬት ላይ ይደርሳሉ።
ከላይ በምስል የሚታየው አለት በጅማ ዞን በየቡ ከተማ የተገኘ ነው።
የተገኘው ድንጋይ ሜትሮይት ወይም ሌላ ዓይነት ከህዋ የተገኘ አለት መሆን አለመሆኑን ለመወሰን የላብራቶሪ ምርመራ አስፈላጊ ነው።
አሁን ባለበት ደረጃ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም።
Meteorites ከተለመዱት የምድር አለቶች የሚጋሩት ነገር ቢኖርም በራሳቸው ደግሞ የተለየ ስሪት እና አወቃቀር ያላቸው በመሆኑ በአይን በማየት ብቻ ለመለየት አዳጋች ይሆናል፡፡
የመስኩ ተመራማሪዎች የሜትሮይትን ስብጥር ለመተንተን የረቀቁ ቴክኒኮችን እና የሳይንስ መመርመሪያ መሳሪያዎችን ይጠቀማሉ።
ይህም የማዕድን ይዘቱን ለመመርመር ከምድር ውጭ ያሉ ንጥረ ነገሮች መኖራቸውን መለየት እና የተረጋጋ የአይሶቶፖች ምጥጥንን (isotope ratio) መለካትን ጭምር ያካትታል።
እነዚህ ትንታኔዎች የሜትሮይትን አመጣጥ እና ስለ መነሻ ምንጫቸው አስመልክቶ ግንዛቤ ለማግኘት ይረዳሉ።
ሜትሮይት በምድር ላይ የሚያስከትሉት ተጽእኖ እና ጉዳት በአንፃራዊነት እጅግ አነስተኛ ነው፡፡
በየዓመቱ ወደ ምድር ገጽ የሚወርዱትም በቁጥር ጥቂት ናቸው፡፡ አብዛኛው አካላቸው በምድር ከባቢ አየር ውስጥ ሲያልፍ ተቃጥሎ ስለሚያልቅ፤ የሚያደርሱት ጉዳት ያነሰ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጉልህ የሆነ ውድመት ሊያስከትሉ የሚችሉት በሚሊዮን አንዳንዴም በሺህ ዓመታት የሚከሰቱት ብቻ ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ቴሌስኮፖችን በመጠቀም ካለማቋረጥ እንቅስቃሴያቸውን በንቃት በመከታተል ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉትን አስቀድሞ በመለየት የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ።
ለምሳሌ ፦ በሀገራችን አቆጣጠር ከ5 ዓመት በኋላ ማለትም በሚያዝያ ወር 2021 ዓ.ም. አፓፊስ (Apophis) የተሰኘ 340 ሜትር ስፋት ያለው አስትሮይድ Geosynchronous ሳተላይቶች ካሉበት 35, 786 ኪ.ሜ. ከፍታ ዝቅ ብሎ ከመሬት በ31, 860 ኪ.ሜ. ከፍታ ላይ እንደሚደርስ ትንበያዎች ያሳያሉ።
የሰው ልጅ የተለያዩ መሳሪያዎችን እና ቴክኒኮችን በመጠቀም ህዋን መመርመር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ይህንን ያክል ግዙፍ አለት ወደ መሬት ሲጠጋ የመጀመሪያው ክስተት እንደሆነ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የአስትሮይድ እንቅስቃሴን ለመከታተል (Asteroid Tracking) የሚያስችል የቴሌስኮፕ ግንባታ እያከናወነ ይገኛል፡፡ "
#EHRC
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ዓመታዊ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ሪፖርት ይፋ ያደርጋል።
የዛሬው ሪፖርት ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት የሚቀርብ ነው።
ሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው፡፡
ይኸው ሪፖርት በሚሸፍነው ጊዜ የነበረውን የሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ጠቅለል ባለ መልኩ ይቃኛል።
በትኩረት ዘርፎች (Thematic Areas) የተስተዋሉ እና የተለዩ ቁልፍ እመርታዎች፣ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች፣ ተግዳሮቶች እና ምክረ ሐሳቦችን ጨምሮ ልዩ ትኩረት የሚሹ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችም ተካትተዋል።
ላለፉት ዓመታት በርካታ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶችን ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ሲመሩ የቆዩት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የሥራ ጊዜያቸው በማብቃቱ ዛሬ ይሰናበታሉ።
(ዓመታዊ ሪፖርቱ እንደደረሰን እንልክላችኋለን)
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ታሳሪዎች ምን አሉ ?
" 4 ኪሎ ተቀምጦ ' ጉዞ ወደ 4 ኪሎ' ከሚሉ 4 ኪሎ ተቀምጠው ጉዞ ወደ ፓርላማ እያሉ በሰላም ቢታገሉ ችግር የለብኝም " - ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ፦
" እስረኛ መፍታት ላይ እኛ እንታማለን ? ' እንዴት እስረኛ ትፈታለህ ? ' ተብለን ስንገመገም እና ስንወቀስ እንዳልነበረ።
ያልፈታነው ጉድ አለ እንዴ ? እስር ቤቱን በሩን ከፍተን ነው የለቀቅነው። በዚህ እንኳን አንታማም።
ከዚህ ፓርላማ የታሰሩት ወንድማችንን በተመለከተ (አቶ ክርስቲያንን ማለታቸው ነው) ሁሉም ተቃዋሚ የሚታሰር ከሆነ ጠያቂዬ (አቶ አበባውን ማለታቸው ነው) ለምን አልታሰሩም ?
ጠያቂዬ ተቀምጠው እየጠየቁ ነው እዚህ።
እርሶን የሚያስቀምጥ እሳቸውን የሚያሳስር ነገር ካለ ልዩነት አለ ማለት ነው። ልዩነቱን ግን እኔ ዳኛ አይደለሁም። ወንጀለኛ ናቸው ፣ ጥፋተኛ ናቸው ልል አልችልም። የፍትሕ ስርዓቱ አይቶ መርምሮ ፈትሾ ፍርድ ይስጥ።
የግል ምኞትህ ያሉኝ እንደሆነ እርሶም እርሳቸውም ከእርሶ ጎን ተቀምጠው ባያቸው ደስታውንም አልችለውም።
በሰላማዊ መንገድ 4 ኪሎ ተቀምጦ ' ጉዞ ወደ 4 ኪሎ' ከሚሉ 4 ኪሎ ተቀምጠው ጉዞ ወደ ፓርላማ እያሉ በሰላም ቢታገሉ ችግር የለብኝም።
የግል ጥላቻ የለኝም። የግል መግፋትም የለብኝም።
ህግ ከፈታቸውና ከኛ መካከል ቢሆኑ ደስታውን አልችለውም። ነገር ግን ሁላችንም ማወቅ ያለብን ፦
- የፓርላማ አባል መሆን
- ጋዜጠኛ መሆን
- ሚኒስትር መሆን
- ማዕከላዊ ኮሚቴ መሆን ከወንጀል እና ከጥፋት አይታደገንም። አለማጥፋት ነው።
የኔ ዋስትና አለማጥፋት ነው። ካጠፋው እመጣለሁ ያለመከሰስ መብቴ ይነሳል እጠየቃለሁ።
እዚህ አካባቢ ላይ መቀመጥ ለማንኛውም ጥፋት ዋስትና አድርገው ፤ ዝም ብሎ መንገደኛ ይነሳና ዩትዩብ ከፍቶ ጋዜጠኛ ነኝ የሚለው እንደዛ ትክክል አይደለም።
ጋዜጠኛም ህግ አለው ፣ ወታደርም ቢሆን ህግ አለው መጠየቅ አለበት ፣ ሚኒስትርም ህግ አለው።
በዚህ አግባብ ማየት ካልቻልን ስራችንን ቆርጠን ጥለነው በኋላ የማንጠግነው ነገር ይፈጠራል። "
#HoPR
" ... ማንኛውም መንግስታዊ አገልግሎት የሚገኘው በገንዘብ እና በእጅ መንሻ ሆኗል " - የም/ቤት አባል
የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምን ጠየቁ ?
አቶ አብርሃም በርታ (የተ/ም/ቤት አባል) ፦
" ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባወጡት ሪፖርት ሙስና በሀገራችን ከአመት አመት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያሉ።
ይህን ስር የሰደደ መንግሥታዊ ሌብነት ወይም ሙስና ለመዋጋት ብሔራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ መቋቋሙን ብንሰማም አርቂ ስራ ሲሰራም ሆነ በሙስና ምክንያት ያንዣበበውን ሀገራዊ አደጋ ለመቀልበስ እርባና ያለው ስራ ሲሰራ አልታየም።
በአጠቃላይ መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት ይሄ ነው የሚባል መፍትሄ እየሰጠ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ቁርጠኝነቱም ላይ ጥያቄ ይነሳል።
ምክንያቱም የህዝብ እና የመንግስት ሀብት በዘረፉ ሙሰኛ ባለስልጣናት ላይ መቀጣጫ የሚሆን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ተጨማሪ ሹመት እና የቦታ ዝውውር በመስጠት መንግስት ሙሰኞችን አብሮ አቅፎ ይኖራል ማለት ይቻላል።
ከዚህ የተነሳ ፦
➡ የመንግስት መዋቅር በሌቦች ተጠልፏል።
➡ ማንኛውም መንግስታዊ አገልግሎት የሚገኘው በገንዘብ እና በእጅ መንሻ ሆኗል።
➡ ዜጎች የዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት በአደባባይ ገንዘብ እየተጠየቁ ነው።
➡ ከፍተኛ የሀገር ሀብት ከሀገር ወጥቶ እየሸሸ ነው።
➡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እያባከኑ ነው።
➡ በኦዲት ሪፖርት መሰረት በየመ/ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ይታያል።
➡ መ/ቤቶች ገንዘብ ያለማስረጃ ወጪ በማድረግ ይጠቀማሉ ፣ ምንም ማስረጃ ሳያቀርቡ በወጪ ይመዘግባሉ፣ ከፋይናንስ መመሪያና ደንብ ውጭ የገንዘብ ክፍያ ይፈጸማል።
እንደሚታወቀው ብዙ ሀገራት ለችግሩ በሰጡት ትኩረት የማያወላውል እርምጃ ስለወሰዱ ችግሩን ማቃለል ችለዋል።
ለምሳሌ በቅርቡ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ለልምድ ልውውጥ የጎበኟቸው የእስያ ሀገራት እነ ሲንጋፖር ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ ስንመለከት ለእድገታቸው ዋናው መሰረት በሙስና ላይ ያላቸው ቁርጠኝነት ነው።
በሀገራችን የሌብነት ችግር ለመቅረፍ አፋጣኝ እና አስተማሪ የሚሆን እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር የጸረ ሙስና ህጋችንን አሻሽለን ቢሆን በሀገራችን አሁን የምናያቸው ፈተናዎች ተደምረው ሙስና የሀገራችንን ህልውና መፈተኑ አይቀርም።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር በህዝቡ የሚቀርበው ተደጋጋሚ ቅሬታና የጄነራል ኦዲተር መ/ቤት በማስረጃ አስደግፎ ያቀረበልን ስር የሰደደ የሙስናን ችግር ለመቅረፍ መንግስትዎ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው ?
በተደጋጋሚ እንደታዘብነው ቃል ከመግባት ባለፈ ምን ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ታስቧል ?
ህዝቡስ ከመንግስትዎ ምን ይጠብቅ ? "
#Ethiopia
#የጤናባለሙያዎች
° “ የ3 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተሰጠንም ” - የጤና ባለሙያዎች
° “ ለጉዳዩ ምላሽ መስጠት ያለበት ወረዳው ነው ” - የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ
° “ የጀበት ችግር ገጥሞን ነው ” - የኪንፋዝ በገላ ጤና ጽ/ቤት
በአማራ ክልል፤ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኪንፋዝ በገላ ወረዳ የሚገኙ ጤና ባለሙያዎች ከሚያዚያ 2016 ዓ/ም ጀምሮ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል አማረዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ፣ “ የ3 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተሰጠንም። ስንጠይቃቸውም ‘ አንከፍልም ’ ነው የሚሉት ” ብለው፣ ክፍያው እንዲፈጸምላቸው ጠይቀዋል።
የቅሬታ አቅራቢዎቹ ብዛት ከ30 በላይ እንደሆነ፣ የክፍያ መጠኑ እንደዬደረጃቸው እንደሚለያይ ገልጸው፣ ይህ ቅሬታ የተፈጠረው ፦
- በስላሬ
- በጭቅቂ
- በሮቢት በገላ በተሰኙ 3 የወረዳው ጤና ጣቢያዎች መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች የጤና ኤክስቴንሽን፣ ጤና ሙያተኞች ደህንነታችን ዋስትና ሳይሰጠው ‘ የክትባት ዘመቻ ካልዘመታችሁ ’ እየተባልን በስጋት ውስጥ ነው ያለነው ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎቹን ቅሬታ ይዞ የዞኑን ጤና መምሪያ አነጋግሯል።
ለምን ብራቸውን አትከፍሏቸውም ? ስንል ለጠየቅነው ጥያቄ ፤ “ለጉዳዩ ምላሽ መስጠት ያለበት ወረዳ ነው። በወረዳው በጀት ዞን ጤና መምሪያው የሚመለከተው ስላልሆነ ” ብሏል።
ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸው የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ ገ/ህይወት በሰጡት ቃል፣ “ የበጀት እጥረት ገጥሞን ነው ” ብለዋል።
ታዲያ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግራችሁ ነበር ? ለሚለው ጥያቄ፣ “ በሚቀጥው በአዲሱ በጀት ተይዞ ይከፈላቸዋል ” ነው ያሉት።
“ ለዚህም ደግሞ አስተዳደሩ ደብዳቤ ጽፏል። ‘በቀጣይ እከፍላለሁ’ የሚል ” ሲሉ አክለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ባለሙያዎቹ ' የጸጥታ ችግር ባለበት ለክትባት ውጡ ተብለናል ' የሚል ቅሬታ አላቸው፤ ለመሆኑ ይህን ስታደርጉ ለደህንነታቸው ከለላ ታደርጉላቸዋላችሁ ? ሲል ጥያቄ አቅርቧል።
ኃላፊው በምላሻቸው፣ “ የጸጥታ ችግር የሌለበት የለም። ዞሮ ዞሮ ግን በሚቻለው አግባብ የአገር ሽማግሌዎችን ይዘን እንሰራለን ” ነው ያሉት።
የአሜሪካ ኤምባሲ ነገ ለምን ተዘግቶ ይውላል ?
በአዲስ አበባ የአሜሪካ አሜባሲ ነገ ሀሙስ ሙሉ ቀን ተዘግቶ ይውላል።
የሚከፈተውም በነጋታው አርብ ዕለት ነው።
ኤምባሲው ተዘግቶ የሚውለው የሀገሪቱን የነጻነት ቀን ለማክበር ነው።
አሜሪካ በየአመቱ እኤአ ሃምሌ 4 ላይ የነጻነት ቀኗን ታከብራለች።
ሀገሪቱ እኤአ በ1776 በኢትዮጵያ አቆጣጠር ደግሞ በ1769 ዓ.ም ነው ከብሪታንያ ቅኝ ግዛትነት ነጻነቷዋን ያወጀችው።
በአዳማ ከተማ ፤ በቦኩ ሸነን ክፍለ ከተማ ሀሮሬቲ ወረዳ እና ቶርበን ኦቦ ወረዳ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የሰው ሕይወት ማለፉና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን ለመስማት ችለናል።
በነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ እንዲቀሰቀሰ ምክንያት የሆነው የከተማ አስተዳደሩ በወረዳዎቹ የሚገኙ ቤቶችን ሕገ-ወጥ ናቸው በሚል የማፍረስ ሂደት ሊጀምር ሲል መሆኑን ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ይፈርሳሉ ያሏቸውን ቤቶች በቀይ ቀለም " X " እያረጉ እንደነበር እና ዛሬ ለማፍረስ ሲመጡ ነዋሪዎች ተቃውሞ እንዳነሱ ይህን ተከትሎም የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ መክፈታቸውን አንድ የዐይን እማኝ አስረድተዋል።
ቦታዎቹ ላለፉት ዓመታት ግብር ሲከፈልባቸው የነበሩ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
ቃላቸ የሰጡ የአከባቢው ነዋሪ እንዳሉት " በተቀሰቀሰው ግጭት እኔ ያያሁት 3 ሰዎች ሞተዋል እና የቆሰሉ ሰዎችም ነበሩ። በዛ አከባቢ ከሰዓት በኋላ እንቅሰቃሴ አልነበረም። ሁሉም ሰው በቤቱ ውስጥ ተቀምጧል እና በአጠቃላይ ያለውን ነገር ማወቅ አልቻልንም " ሲሉ ገልጸዋል።
ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያገኘናቸው ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ የያዙ በርካታ ሰዎች ተቃውሞቸውን ለማሰማት መንገድ በመዝጋት እና " ፈረሳው ይቁም !! " የሚሉ መፈክሮች እየሰሙ እንደነበር ነው።
በሌላ አንድ ቪዲዮ ላይ ነዋሪዎቹ በዱላ እንዲሁም በድንጋይ መንገድ ዘግተው እንደነበር ተመልክተናል።
ነዋሪው ተቃውሞውን ማሰማት በጀመረበት ወቅት ተኩስ መጀመሩና በሰልፍ ላይ የነበሩ ሰዎች ሲበታተኑም ተመልክተናል።
በዚህ ውስጥ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ከዐይን እማኞች መስማት የቻለን ቢሆንም ምን ያህል ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ማረጋገጥ አልተቻለም። ከከተማው አመራርና የጸጥታ አካላት ጉዳዩን ለማጣራት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
#Ethiopia
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፥ አቶ ካሳሁን ጎፌን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አድርገው ሾሙ።
ወ/ሮ ሽዊት ሻንካን ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ቀጀላ መርዳሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶች እና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ከዛሬ ሰኔ 26 /2016 ዓ/ም ጀምሮ እንደ ተሾሙ ታውቋል።
#Ethiopia🕊
ቅዱስነታቸው ሁሉም ለሰላም በአንድነት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ።
" የሃይማኖት ተቋሞቻችን ለዘላቂ ሰላማችን " በሚል ርእስ በአዲስ አበባ አንድ መድረክ ተካሂዷል።
በዚህም መድረክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወክጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቅዱስነታቸው ፤ " ጥላቻ፣ ጦርነት፣ ጠብ፣ ክርክር፣ ሞኝ መሆኑን እያወቅን እዚያ ላይ እንንከባለላለን። የሰው ልጅ ህልውናውን ለመጠበቅ ሰላምን መምረጥ እና መከተል ይኖርበታል " ብለዋል።
" የሰላምን እጦት ያመጣነው ራሳችን ነን። ማንም አምጥቶ አልጫነብንም " ያሉ ሲሆን " ሰላም ከሌላ መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ተቋማት ምንም መሰራት እንደማይችሉ አውቀን ለሰላም በአንድነት መቆምና ሰላምን መከተል ይኖርብናል " ሲሉ ተናግረዋል።
" ለዚህም ሁላችንም ከቀደመው እየተማርን መጪውን ሰላማዊ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል " ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ፥ " የሔድንበት መንገድ ጎድቶናል ስለሆነም ወደ ሰላም እንመለስ ብለን መወሰን አለብን። ለዚህም ሁላችንም ወደ አእምሮችን ተመልሰን ሰላምን እንከተላት " ሲሉ አባታዊ ጥሪ አቅርበዋል።
#EOTC
#Ethiopia
#Tigray #Mekelle
ባለፉት 11 ወራት ብቻ በመቐለ 12 ሴቶች ሲገደሉ 80 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል።
የመቐለ ፓሊስ ከሀምሌ 2015 ዓ/ም እስከ ሰኔ 2016 ዓ/ም ባሉት 11 ወራት ግድያ ጨምሮ 4,340 ከባድና ቀላል የወንጀል ተግባራት በከተማዋ እንደተፈጸሙ አሳውቋል።
የተፈፀሙት ከባድና ቀላል ወንጀሎች በቁጥር ፦
➡️ የሴቶች ግድያ 12
➡️ አስገድዶ መድፈር 80
➡️ ስርቆት 1,953
➡️ ድብደባ 583
➡️ ዝርፍያ 349
➡️ የመገደል ሙከራ 178
➡️ እገታ 10
ፖሊድ ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዙ 170 የፓሊስ ኮሚኒቲዎች መቋቋማቸውን ገልጿል።
እየተፈፀሙ ያሉ የወንጀል ተግባራት ያልተለመዱ ናቸው ያለው ፖሊስ የሚፈጸሙትን ወንጀሎች ለመቆጣጠር ከወትሮው በተለየ የህብረተሰብ ተሳትፎ እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝቧል።
#Update #DireDawa
በድሬዳዋ ከተማ አሸዋ የገበያ ስፍራ የተከሰተው እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።
በተለምዶ ' አሸዋ ' በመባል በሚጠራው የገበያ ስፍራ ዛሬ ጠዋት ተነስቶ የነበረው የእሳት አደጋ፥ በርካታ የመሸጫ ሱቆችና ማሽላ ተራ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በስፍራው ተገኝተው ሁኔታውን ተመልክተዋል።
የአደጋውን መንስኤና የጉዳት መጠን በምርመራ በማጣራት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የእሳት አደጋው ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ርብርብ ላደረጉ ነዋሪዎች የጸጥታ ኃይል ምስጋና አቅርበዋል።
#AddisAbaba
የሁለት ዓመቷን ሶሊያና ዳንኤል የተባለችውን ህፃን በመጥለፍና በከባድ ስርቆት ወንጀል የተከሰሰችው ግለሰብ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጥታለች።
የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባት ቤዛዊት በቀለ የተባለችው ግለሰብ በሰራተኝነት ተቀጥራ ስትሰራበት ከነበረበት ቤት (ሳሪስ አዲስ ሰፈር) መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ/ም ህጻን ሶሊያናን ይዛ በመሰወር ሱሉልታ ከተማ " ኖኖ መና አቢቹ " ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ህፃኗን ሸሽጋ በተቀመጠችበት በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋሏን ይታወሳል።
ግለሰቧ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኃላ የአ/አ ፖሊስ ምርመራ የማስፋት ስራ በመስራት ከዚህ ቀደም በቤት ሰራተኝነት ከተቀጠረችባቸው አምስት የተለያዩ ቤቶች ልዩ ልዩ ንብረቶችን መስረቋን አረጋግጧል።
ከሰረቀቻቸው ንብረቶች መካከልም 2 ላፕቶፕ ፣ 1 ሞባይል ስልክ እና ሌሎች የተለያዩ ዕቃዎች ፖሊስ ባደረገው ጥረት ከሸጠችበት በምሪት እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
በግለሰቧ ላይ ምርመራ ተጣርቶ በከባድ ስርቆት እና ህፃን ልጅ መጥለፍ በሚል ወንጀል በአቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተ በኋላ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ቤዛዊት በቀለ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
#AddisAbabaPolice
#Ethiopia #Somalia
" ልዑካኑ የቀጥታ የፊት ለፊት ንግግር / ውይይት አላደረጉም " - የሶማሊያው ፕሬዜዳንት
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አሸማጋይነት ትላንት አንካራ ውስጥ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል።
በቱርክ ጋባዥነት በተደረገው ውይይት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞሊም የመሯቸው ልዑካን አንካራ ተገኝተው ነበር።
ከውይይቱ በኃሏ የሶስቱ ሀገራት የጋራ መግለጫ ወጥቷል።
መግለጫው ፥ ሚኒስትሮቹ ያላቸውን ልዩነቶች ለሁለቱም ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት ያሉ ሁኔታዎችን እንደዳሰሱ ገልጿል።
ሚኒስትሮቹ በተናጥል በግልጽነት ፣ ወዳጅነት ባለው እና የወደፊቱን ያለመ ውይይት እንደነበራቸው ነው የተመላከተው።
ሁለቱ አገራት ችግሮቻቸውን ለመፍታትና ቀጣናው እንዲረጋጋ የጀመሩትን ውይይት ለመቀጠል ተስማምተዋል የተባለ ሲሆን ለሁለተኛ ዙር ውይይት በአንካራ ነሐሴ 27/ 2016 ዓ.ም እንደሚገናኙ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ከ6 ወራት በፊት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ በይፋ ተገናኝተው ሲመጋገሩ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
የጋራ መግለጫው ሁለቱ አገራት ልዩነታቸውን ለሁለቱም ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ ለመፍታት ያሉ ሁኔታዎችን እንደዳሰሰ ቢገልጽም እነዚህ ተቀባይነት አላቸው ስለተባሉ ጉዳዮች የተጠቀሰ ጉዳይ የለም።
በሌላ በኩል ፥ የሶማሊያው ፕሬዜዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐሙድ ትላንት ውይይቱ ካበቃ በኃሏ ባሰሙት ንግግር ፦
- ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ከተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ወደኋላ የምትመለስበትን ምንም ምልክት አላሳየችም፤
- ከያዘችው መንገድ እየተመለሳች ስለመሆኑ ምንም ምልክት የለም ፤
- አንካራ ውስጥ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ልዑካን ቀጥተኛ ንግግር አላደረጉም ይልቅም ቱርክ በመሃል እንደ አስታራቂ ሆና እየሰራች ነበር ብለዋል።
ከሰሞኑን የኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ መ/ቤትን ሎጎ በመጠቀም አንካራ ውስጥ በተደረገ ውይይት " ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ሰርዛለች " የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር።
#Ethiopia #Somalia #Turkey
#National_GAT
ብሔራዊ የድኅረ ምረቃ መግቢያ ፈተና (GAT) መቼ ይሰጣል ?
የ2016 የድኅረ ምረቃ መግቢያ ፈተና (GAT) ሐምሌ ወር መጨረሻ ሳምንት ይሰጣል።
አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል የ3ኛ ዙር አገር አቀፍ የድኅረ ምረቃ መግቢያ ፈተና (GAT) በሐምሌ ወር የመጨረሻ ሳምንት እንደሚሰጥ አሳውቀዋል።
የ2ኛው ዙር የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች የመግቢያ ፈተና በህዳር 2016 ዓ.ም መሰጠቱ ይታወሳል።