ethiohumanity | Education

Telegram-канал ethiohumanity - ስብዕናችን #Humanity

30703

🔆እየጠየቁ መኖር መልስን፣ መልስን ፈልጎ ማግኘት ዕውቀትን፣ እውቀት ነፃነትን፣ ነፃነት ሙሉ ስብዕናን፣ ሙሉ ስብዕና ሠላምና እርካታን፣ እርካታ ደግሞ ደስተኛ ሆኖ መኖርን ያስገኛል፡፡ አብረን እንደግ !! @EthioHumanity @Ethiohumanity ✍የተሰማቹን አጋሩን! ቤቱ ሁሌም ክፍት ነው፣ሃሳባቹን ፃፍፍ አርጉልን @EthioHumanitybot

Subscribe to a channel

ስብዕናችን #Humanity

📍በሱፊዎች ዘንድ የሚነገር አንድ ታሪክ አለ..

♦️በስቃይ የተሞላ ህይወትን የሚመራ አንድ ሰው ነበር... ሰውዬው ወደ አምላኩ በሚጸልይበት ጊዜ ሁሉ "ሁሉም ሰው ደስተኛ ሆኖ እየኖረ ለምንድነው እኔ ብቻ የምሰቃየው?" እያለ ይጠይቅ ነበር፡፡

አንድ ቀን ጥልቅ በሆነ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆኖ ለአምላኩ እንዲህ ሲል ጠየቀ... "አምላኬ የማንኛውንም ሰው ስቃይ ብትስጠኝ ልቀበል ዝግጁ ነኝ... እባክህ የእኔን ግን ውሰድልኝ... ከዚህ በላይ ልሸከመው አልችልም" ብሎ ተማረረ፡፡

ጸሎቱን ጨርሶ እንደተኛ ታዲያ ውብ የሆነ ህልም አየ... በህልሙ ውስጥ አምላክ ሰማይ ላይ ተከስቶ እንዲህ ሲል ይደመጣል... "ስቃያችሁን ሁሉ ወደ ቤተ መቅደሱ አምጡ..."

እያንዳንዱ ሰው የየራሱ ስቃይ ያታከተው ስለነበር "የማንኛውንም ሰው ስቃይ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፤ የእኔን ግን ውሰድልኝ፤ ከዚህ በላይ መሸከም አልችልም" ብሎ ይጸልይ ነበር...

🔺በዚህም ምክንያት ሁሉም ሰው ስቃዩን በቦርሳ አጭቆ ወደ ቤተ መቅደሱ አመራ... ባለታሪኩን ጨምሮ ሁሉም ሰው ጸሎቱ በአምላኩ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘለት በስፍራው ላይ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ነግሶ ነበር...

💡ከቤተ መቅደስ ሲደርሱ አምላክ እንዲህ ሲል እወጀ... "ቦርሳችሁን ከግድግዳው ስር አስቀምጡት"... ሁሉም ሰው ቦርሳውን አስቀምጦ ጨረሰ... አምላክም እንዲህ ሲል በድጋሚ አወጀ... "አሁን መምረጥ ትችላላችሁ፤ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ቦርሳ መውሰድ ይችላል"...

🔺በዚህ ጊዜ ቀን ከሌሊት 'የማንኛውንም ሰው ስቃይ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ' እያለ ሲጸልይ የነበረው ሰውዬ ሌላ ሰው የእርሱን ቦርሳ እንዳያነሳበት እየተጣደፈ ወደ ራሱ ቦርሳ ሄደ... ሁሉም ሰው እንደ ሰውዬው ሁሉ የየራሱን ስቃይ ያጨቀበትን ቦርሳ ፍለጋ ተራወጠ... በሚያስገርም ሁኔታ እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ስቃይ በድጋሚ ለመሸከም ዝግጁ ነበር...

ምንድን ነበር የተከሰተው?...

💡በህይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ አንዳቸው የሌላኛቸውን ችግር ስቃይና መከራ ተመለከቱ... እንዲያውም ከራሳቸው የሚበላልጡ፣ የሌሎች ሰዎች ስቃይ የታጨቀባቸው ትላልቅ ቦርሳዎች እንዳሉም ተገነዘቡ... በዚህ ላይ ሁሉም ሰው ከራሱ ስቃይና መከራ ጋር ተላምዷል... የራሱን ስቃይ ማባበልና መቻል አይቸግረውም... የሌላውን ሰው የመከራ ቦርሳ ቢወስድ ግን ከቦርሳው ውስጥ ያለው አዲስ አይነት መከራ ምን አይነት እንደሆነ አያውቅም... ምናልባት የባሰም ሊሆን ይችላል...

አላሚው ሰው ከእንቅልፉ ሲነቃ በድጋሚ ጸለየ... "አምላኬ ስላሳየኸኝ ህልም አመሰግንሃለሁ...ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነቱን ጥያቄ ደግሜ አልጠይቅህም... የሰጠኸኝን ነገር ሁሉ የሰጠኸኝ በምክንያት ነው" ሲል ተናገረ...

📍የቅናት ስሜት ካለባችሁ በማያቋርጥ ስቃይ ውስጥ ትወድቃላችሁ፤ የምትቀኑ ከሆነ ሀሰተኛ ትሆናላችሁ፤ ማስመሰልም ትጀምራላችሁ፤ ያልሆናችሁትን መስላችሁ ለመታየትም ትሞክራላችሁ... የሆነ ሰው ጋር ኖሮ እናንተ ጋ የጎደለ ነገር ያለ ሲመስላችሁና ነገርዬውን ማግኘት የማትችሉ ከሆነ ከሰው ላለማነስ ብላችሁ የረከሱ ነገሮችን ማበጀት ትጀምራላችሁ...

💡ለቀናተኛ ሰው ህይወት ሲኦል ትሆንበታለች... ስለሆነም ቅናታችሁ ይጠፋ ዘንድ ራሳችሁን ከሌላው ጋር ማነጻጸር አቁሙ... ይህን ስታደርጉ ያልሆናችሁትን መስላችሁ ለመታየት የምታደርጉትን ጥረትና ሌላውን ለመምሰል የምታደርጉትን ሙከራ ታቆማላችሁ...

🔑ይህ ሁሉ ሂደት የሰመረ የሚሆነው ግን ውስጣዊውን ሀብታችሁን ማሳደግ ስትችሉ ነው... ለማደግ ጣሩ... ይበልጥ እውነተኛ ግለሰብ ለመሆን ሞክሩ... እራሳችሁን አፍቅሩ... ለራሳችሁ ክብር ስጡ... ይህ ሲሆን የገነት በሮች ክፍት ይሆኑላችኋል... በእርግጥ ወደ በሮቹ ተመልክታችሁ ስለማታውቁ ነው እንጂ እስካሁንም በሮቹ ክፍት ነበሩ...

✍ ደምስ ሰይፉ

ውብ ቅዳሜ❤️

@EthioHumanity
@BridgeThoughts

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

💎እንደ ወርቅ እንደ አልማዝ ሁኑ

ወርቅና አልማዝ ውድ ናቸው። የትም አይገኙም። ብዙ ተቆፍሮ፣ ተለፍቶ ነው የሚገኙት። የትም በቀላሉ የምትገኙ አትሁኑ። የራሳችሁን ዋጋ እንደ ወርቅ፣ እንደ አልማዝ ውድ የምታደርጉት ራሳችሁ ናችሁ። ለጠራችሁ ሁሉ አቤት፣ እንሂድ እንጂ ላላችሁ ሁሉ ወዴት አትበሉ።

💡Rarity [አለመገኘቱ] ብቻ ግን በቂ አይደለም። ወርቅና አልማዝ ጌጥ ናቸው። ያምራሉ። ወርቅ የቀይ ቢጫ ውብ መልክ አለው። አልማዝ በባህሪው colorless ከለር አልባ ነው። አልማዝ ብዙ አይነት ቀለም ይዞ የምናገኘው በውስጡ ካሉት impurities የተነሳ ነው። ግን መሰረታዊ ውበቱን አይቀንሱትም። የሰው ልጅ ውበት ንጽህና ነው። ንጹህ አካል፣ ንጹህ መንፈስ፣ ንጹህ አስተሳሰብ!!

📍አንድ ነገር በቀላሉ የማይገኝ ብቻ መሆኑ ተፈላጊ አያደርገውም። ዋናው ጉዳይ ባህሪያቶቹ ናቸው። የወርቅ በጣም ተፈላጊ ባህሪ ወርቅ አይዝግም። እንደ Iron ብረት ከሆንን ወደ ውስጣችን ሰርጎ የገባው ውሃ ሁሉ ያዝገናል። መንፈሳችንን ይረብሸዋል። ወርቅ ሁኑ። ወርቅ ሚሊየን አመት ውሃ ውስጥ ቢቀመጥ አይዝግም። በዚያ ላይ malleable ተዛዥ ተጣጣፊ ነው። እንደ ወርቅ ሊቀጥን የሚችል ሌላ ኬሚካል ኢለመንት የለም።

💡አልማዝ ደግሞ በጣም ጠንካራ ነው። ማንኛውንም ነገር በብቃት መቁረጥ ይችላል። በነገራችን ላይ አልማዝና ከሰል አንድ ናቸው ደግሞም አይደሉም። አንድነታቸው ሁለቱም የተሰሩት ካርበን ከሚባል ኢለመንት መሆኑ ሲሆን ልዩነታቸው እነዚህ የካርበን አተሞች በአልማዝና ከሰል ውስጥ ያላቸው ኬሚካል ስትራክቸር ነው። ከሰልን ወደ አልማዝ መለወጥ በብዙ ፓስካል ፕሬዠር [Pascal Pressure] ወይም ብዙ ግፊትና እና ብዙ ኬልቪን [Kelvin] ሙቀት ያስፈልጋዋል።

📍ውስጣችን ያለው ማንነት ካርበን ነው። ከሰል ወይም አልማዝ ማድረግ የኛ ፋንታ ነው። የህይወት ፈተና የከሰል ማንነታችንን ወደ አልማዝ የሚቀይር እርሾ ግፊት ነው። እነዚህ የወርቅና የአልማዝ ኬሚካላዊ ባህሪያት ብዙ ኢንደስትሪያል ጠቀሜታ አላቸው። ወደዚያ በዝርዝር አንገባም። አሁን የምንወስደው ከወርቅና ከአልማዝ ለህይወት የሚጠቅመንን ብቻ!

✍ ቴውድሮስ ሸዋንግዛው

ውብ ሰንበት❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanitybot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

💚ንቁ የሃሳብ ሰው ስንሆን የምንሰራው ዓለምን ነው። ለዚህ ደሞ የስብዕና ግንባታ ወሳኝ ነው ብሎ ያምናል ቻናላችን. . ታድያ ሁሉን አልፈን በአብሮነት ከእናንተ ጋር ተያይዘን አሁን ላይ ደርሰናል።

💛ከጎናችን በመሆን አጋርነታቹን እደምሰሶ ላፀናቹልን ቤተሰቦቻችን ልባዊ ምስጋናችን በያላችሁበት ይድረሳችሁ !!

❤️ዛሬም እደትናንቱ ታስፈልጉናላቹ ፣ ወድ ሀሳብ አስተያየታችሁ ለኛ ትልቅ ግብአቶቻችን ናቸው። ሁላቹሁም ሀሳብ አስተያየት እንድታደርሱን በአክብሮት እንጠይቃለን።

የሚሰማችሁን እዚች ላይ ፃፍፍ አርጉልን
               👉 @EthiohumanityBot
               👉 @EthiohumanityBot

✍ሁሉም የለንምና በእናንተ ሀሳብ  
           የጎደለውን እንሞላለን!!

    ከልብ እናመሰግናለን ❤️

@EthioHumanityBot @EthioHumanityBot
 

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

💡በየትኘውም የህይወት መንገድህ መልካም ስብዕናን አየዘራህ ስትጓዝ ባታይውም ለሌሎች ፍካት ሆኖ ይቆያል ።ደግነትህ ለብዙዎች የዕድሜ ማራዘሚያ ሰበብ ስለሆነ እንዳይከስም ጠብቀው። ለጋስ በመሆንህ በምላሹ ከሌሎች ምንም ነገር አትጠብቅ። የጊዜ ጉዳይ ቢሆን እንጂ መልካም ነገር ሁሌም ከፈጣሪህ በጎ ምላሽ አለው።

📍ህሊናህ ይረካ ዘንድ ከመቀበል ይልቅ ሰጪ ሁን። በምግባርህ ፈጣሪህን ለማስደሰት ሁሌም ጥረት አድርግ። እርሱ ከወደደህ ደስታ በእጅህ ትገባለች። በመልካም ስነ ምግባር ሽቶ የተርከፈከፈ ስብዕና ከመሬት በታች አፈር ለብሶ እንኳ መዓዛው ያውዳል።

💡አስተሳስብህ ካለባበስህ የበለጠ ሲያምር መልካምነትህ ከምትቀባው ሽቶ የበለጠ ሲያውድ ስነምግባርህ ከመልክህ የበለጠ ሲያምር የዝነጣ ጣሪያ ላይ ደርሰሀል ማለት ነው። ላመነን ሰው መታመን ከህሊና ወቀሳ መዳን ነው። ማንን እንደምታገኝ አታውቅምና ለሁሉም ሰው ቅን ሁን፡፡ በህይወታችን የምናሰፍራቸው ነጥቦች ሁሉ በኋላ ላይ ተያይዘው መስመር መስራታቸው አይቀርም።

  ውብ አዳር❤️

@Ethiohumanity
@EthioHumanity

@EthiohumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🔴የሕይወት ግንድ ብዙ ቅርንጫፎች ነን!!

📍 አንድ ውቅያኖስ ላይ ነን  ‘የአንተ’ ታንኳ ሲናጥ ‘የእኔው’ ደንገል መንቀጥቀጥ ይጀምራል፣ ‘የእርሷ’ ጀልባ ሲቀዝፍ የባሕሩ ለመምቴ ይናጣል፣ የሰላምህ እርግብግቢት የሰላማችንን ንፋስ ይጠቅሳል… የሕመማችን ትንፋሽ የደስታ መንፈሷን ይበርዛል።ስለምን - ‘እኔም’፣ ‘አንተም’፣ ‘እርሷም’፣ ‘ሁላችንም' አንድ ነንና።

🔷መምህሩ ራማና ማሃርሺ …
“How are we Supposed to treat others?” ብለው ቢጠይቁት…
“There are no others” ሲል የመለሰው ለዚህ ነበር።

በተገበርከው ክፋት ብቻ ሳይሆን በተብሰልስሎትህ ሂደት ነገር ዓለማችን ይታወካል። በተነፈስከው በጎ ቃል አይደለም ባሰላሰልካት ደግነትም መውጣት መግባታችን ይዋባል… ብቻህን አይደለህምና የብቻ ሰላም የለህም… አልተነጣጠልንምና የብቻ ሕመምም አይኖርህም

የግዙፍ ውቅያኖስ አካል ነን ፣ እኛም ሆንን በዙሪያችን ያለው የተፈጥሮ ስንክሳር የውቅያኖሱ አንድ ጠብታ ነው ፣ አንዲት ጠብታ የምትፈጥረው ለመምቴ /Ripple/ የሌላውን ለመምቴ ትነካለች… እኒህ የሃሳብ፣ የስሜትና የድርጊት ለመምቴዎች በሌላኛው ተፈጥሮ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አላቸው… በበጎም በክፉም… ተመልሰው ግን ወደ ምንጫቸው ይመጣሉ፣ በመዋኛ ገንዳ ውስጥ የፈጠርከው የውሃ ለመምቴ የገንዳውን ግድግዳ ገጭቶ ወዳንተ እንዲመለስ ማለት ነው።

🔶ከኔ ቤት ላይ የረጨኸው እሳት ከሆነ ነበልባሉ ያንተን ቤት ይነካል ፣ ሽቶ ስትረጨኝ የመዓዛው ቅንጣቶች ለአፍንጫህ ውብ ጠረን ይለግሳ፣ “You reap what you saw”ሰው የዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳል ፣ ይህን ምስራቃውያኑ Karma ሲሉት ሌሎች ደግሞ Boomerang ይሉታል… Boomerang አውስትራሊያኖቹ አቦርጂኒስቶች ከእንጨት የሚሰሩት ደጋን ቅርጽ ያለው የአደን መሳሪያ ሲሆን ወርዋሪው ዘንድ ተመልሶ እንዲመጣ ተደርጎ የሚነደፍ ነው። ለሃሳብ፣ ለስሜትና ድርጊትህ መጠንቀቅ የሚኖርብህ ወላፈኑ ‘ለእኔም’፣ ‘ለእርሷም’፣ ‘ለእነርሱም’ እንደሚተርፍ በማሰብ ነው… ምክንያቱም
We are all One!

🔷ሰው ብቻ ሳይሆን ከዋክብቱ፣ ሕዋው፣ ምድሪቱ፣ እንስሳው… በሚታየውና በማይታየው ዓለም ያለው ነገር ሁሉ በአንዳች ተፈጥሯዊ ክር የተሳሰረ ነው… ማሰሪያው ስላልታየ መተሳሰሩ የለም አይባልም።

‘እዚያ ቤት ሲንኳኳ እኛ ቤት ይሰማል’ ‘ከወዲህ አንተን ሳማ እዚያ ከንፈር ትነክሳለህ’፣ ‘እከሊት ስታነሳኝ በስቅታዬ አውቀዋለሁ’፣ ‘የሰፈር ውሻ ሲያላዝን አንዱ አዛውንት ሊያልፉ ነው ማለት ነው’… ‘ውስጥህ ሲረባበሽ ራቅ ካለ ቤተሰብህ አልያም ወዳጅህ ቤት አንድ አደጋ አለ ማለት ነው’፣ 'ቅንድብህ ሲርገበገብ እንግዳ ሰው ልታይ ነው'፣ የጥንቶቹ ይሄ እውነት ስለገባቸው ይመስለኛል መሰል አባባሎች ያቆዩልን።

♦️በረከት በላይነህ "የመንፈስ ከፍታ" ላይ እንዲህ ይለናል👇

“የግልህ ወንዝ ስለሌለህ ብቻህን የምትሰራው ድልድይ የለም! የሰማዩ ርቀት፣ የምድሪቱ ስፋት በ’እኛ’ እንጂ በ’እኔ’ አይለካም፡፡ ውዱ ‘እኔ’ ከ’እኛ’ የተሰራው ነውና!”

🔷እዚህ ጋ ነው ስለ ዝምድናና ባዳነት ያለን ግንዛቤ መፈተሸ ያለበት፣ ስለ ዘርና ቀለም ያለን መረዳት መጤን ያለበት፣
Peter Russell “The Global brain” ብሎ ባሰናዳው ቪዲዮው ላይ አንድ በጨረቃ ላይ የተጓዘ የጠፈር ሳይንስ ተመራማሪ የተናገረውን ውብ ቃል ትሰማላችሁ
“When you are up there you are no longer an American citizen or a Russian citizen. Suddenly those boundaries disappear. You are a planetary citizen.”

🔑ኑረዲን ዒሳ በአንድ ግጥሙ.

“ባዳውን አፍቅሮ፣
ከባዳው ልጅ ፈጥሮ፣
እኔን ባዳዬ አለኝ - ሰባት ቤት ቆጥሮ፣
ልጁን ዘመዴ አለው - በፍቅር ታውሮ፡፡
ቅጠሉ ነኝና ለረጂሙ ሃረግ፣
እኔም ዘመዱ ሆንኩ - መቼስ ምን ይደረግ?” ብሏል…

❤️ፍቅር ሲገባን የልዩነት ቅዠት ይተናል ፣ ማንነት ሲገባን ሕብራችን ይታያል ፣ ጥበብ ሲያጥጠን ግን ልዩነት ያዜምልናል፣ ፍቅር ስንሰጥ በዙሪያችን ባሉት ላይ እርግብግቢቱ ፍቅርን ይወልዳል፣ክፉ ስናስብ ደግሞ በተቃራኒው ክፋት ይጠነሰሳል፣ከፊልዱ ውጭ እስካልሆንን ድረስ ከምላሹ ተጽዕኖ ልናመልጥ አንችልም።

                             ✍ደምስ ሰይፉ
@bridgeThoughts
ውብ ቻናሉ ነው

         We are all One!
           ውብ ቅዳሜ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

💎የመሰብሰብ ጉጉትህ ላይ እስካልሰለጠንክ ድረስ የሚበቃ ነገር የለም፤ ጊዜ በጨመረ - ቀን በተቆጠረ ልክ የፍላጎት አድማስ እየሰፋ፣ የመጨመር ሃሳብ እየተንሰራፋ ይቀጥላል...

💡የመጨመር ጉጉት ጉድለት ላይ ብቻ ከመቆዘም የሚፈጠር ህመም ነው፤ በቃኝ አለማወቅ ልክን የመሳት አባዜ ነው... ምን 'ሀብታም' ብትሆን በፍላጎትህ ላይ ገዢ እስካልሆንክ ድረስ የደስታን ደጅ አትረግጥም...

📍በሕይወት ውስጥ በቃኝ የማለትን ያህል ምልዓት የለም!! ብዙ ሰው "ያለኝ ይበቃኛል" እያለ ያጣቅሳል - እንደ ጥቅሱ ግን አይኖርም፤ ጥያቄው ታዲያ 'ያለው ስንት ሲሆን ነው የሚበቃው?' የሚለው ነው፤

የኑሮ ቅንጦት የበዛበትም፣ መኖር ቅንጦት የሆነበትም እኩል 'ያለኝ ይበቃኛል' ካለ ልክ አይሆንም... ስሜትም አይሰጥም።

📍ቁምነገሩ 'ያለህ መብቃቱ' ሳይሆን ባለህ መብቃቃቱ ነው... ሁሉም ሰው 'ያለኝ ይበቃኛል' ሲል 'የሚገባውን' ብቻ ይዞ ላይሆን ይችላል... የተትረፈረፈለትም - ትራፊ ያጠጠበትም አንድ ሊሆን አይችልም... ግና የሚብቃቃ ሰው በውስንነት ውስጥ ሆኖም ጉድለት አይሰማውም...

💎ስትብቃቃ ያለህ ምንም ያህል ይሁን ደስታ ሳይርቅህ ትኖራለህ፤ ስታግበሰብስ ግን ምድሪቱ ሙሉ ስጦታ ሆና ብትቀርብልህ እንኳ በቃኝ አያውቅህም...አንተ ዘንድ የበዛው ከሌላው ጎድሎ ነው፤ በማትፈልገው ጊዜ በስብሶ ሳትጥለው በሚፈልገው ጊዜ ለሚጠቀመው ስጠው!!

✍ደምስ ሰይፉ
@BridgeThoughts
[የግል ቻናሉ ነው ተቀላቀሉት ]

ውብ አዳር ❤️

@Ethiohumanity
@EthioHumanity

@EthiohumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🔴 ስኬት የደስታ ቁልፍ አይደለም ይልቁንስ የስኬት ቁልፍ ደስታ ነው ! ምክንያቱም የምንሰራው ስራ ከወደድንው ስኬታማ ና ውጤታማ የማንሆንበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም ፣ ደስታችን ከስኬታችን ያደርሰናል !

🔶በሞያህ ደስተኛ ከሆንክ የምታስበው
ስኬት ወደ አንተ ይመጣል፣ በምትሰራው ነገር ደስተኛ ከሆንክ ከጥሩ ነገር ትሰራለህ ከጥሩ ቦታ ትደርሳለህ ውጤትን ታገኛለህ፣ ስኬት ማለት ያለህበት ቦታ ሳይሆን የምታስበው የምታስበው ነገር ነው ፣ ስዎች ራሳቸው የወሰኑትን አለያም ያሰብትን ያክል ደስተኞች ናቸው !
እያንዳንዱ ሰው የሚደሰተው በዘጋጅው የደስታ መጠን ያክል ነው ።

🔷ደስተኛ የሚያደርግህ ያለህ ነገር ማንነትህ ያለህበት ቦታ አለያም የምትሰራው ስራ ሳይሆን የምታስበው ነገር አስተሳሰብህ ነው ! ምክንያቱም ደረጃህን የሚወስነው አቋምህ ሳይሆን አስተሳሰብህ ስለሆነ !ማንነታችንን ተቀብለን ከራሳችን ጋር ሰላም እስካልፈጠርን ድርስ ባለን ነገር ደስተኞች አንሆንም !

🔶ፈጣሪህን ታመን። ልብ በል ፤ ቤትህን በፍጥነት ሠርተህ መጨረስህ ሳይሆን ንፋስና ጎርፍን መቋቋም የሚችል ጠንካራ አድርገህ መሥራትህ ነው ቁምነገሩ። በሰዎች ደስታ ደስ ይበልህ። የእውቀት ሰውና ጠንካራ ሠራተኛም ሁን! በዕውነት ፣ በሃቅና በራስ አገዝ አዋጭ መንገድ ከተራማድክ እመነኝ በያንዳንዱ እርምጃህ ስኬትህን እየገነባህ ነው።

🔷 ስኬት በቅንነት እንጅ በብልጠት አይደለም ! ሊሆንም አይችልም። አጭበርብሮ ስኬት ከመቆናጠጥ በክብር መውደቅ ይሻላል፣ የምትሔድበት የስኬት መንገድ ሺህ ጊዜ ይርዘም እንጂ ቶሎ ለመድረስ ብለህ አቋራጭ መንገድ አትጠቀም። ልብህ በእውነት ላይ ተረማምደው በሰዎች ትከሻ ላይ ተንጠልጥለው ፣ በአቋራጭ ባደጉ ሰዎች እንዳይቀና! የግፍንም እንጀራ እንዳትበላ ተጠንቀቅ ፣ትግስትን ገንዘብህ አድርጋት አምላክ ለአንተ ያዘጋጀዉ ነገር አለውና።

እናም ወዳጄ

የስኬት መጨረሻ የውድቀት መጀመሪያ እንደሌለ እወቅ ፣ ስኬት በተገኘ ነገር ላይ በመርካት እንደሚለካ አስብ። ስኬትን ከአእምሮ እርካታ ጋር እንጂ ከቁስ ጋጋታ ጋር አታዛመድ፣ የሰው ልጅ እራሱን ሊያስደስት የሚችለው በመልካም ባህሪውና በሚሰራው ጥሩ ሥራ እንጂ የሚያምር መልክና አቋም ወይንም በርካታ ሀብት ስላለው አይደለም ... የሚያምር አቋምህና ሀብትህ ምድር ላይ ቀሪ ናቸው ..መልካም ስራህ ግን ለነገ ስንቅ ይሆንሐል ! ባለህበት  የህይወት ደረጃ መርካት ከቻልክ በራሱ ስኬት እንደሆነ እወቅ።

                ውብ አሁን ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @Ethiohumanitybot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

❤️ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ:-

እንኳን ለጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ !!

በዓሉ፦ የሰላም ፣ የፍቅር፣ የደስታ ፣ የመተሳሰብ ፣ የአብሮነት እና የአንድነት በዓል እንዲሆን እንመኛለን።

  (መልካም ትንሳኤ ፤ መልካም በዓል!)❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

💡ቀላል የህይወት መንገድ  ምርጫህ ሆኖ ጠንካራ፣ ስኬታማና ምርጥ ህይወት የሚኖር ሰው አትጠብቅ።

💡በመከራዎቹ ሁሉ ተፈትኖ እንደወርቅ ቀልጦ የምርጥ ማንነት ባለቤት የሚሆነውን ፣ ጠንካራውን፣ አይበገሬውንና የህይወት መንገድ ነፃነቱን በስኬቱ የሚጎናፀፈውን አንተን ለመተዋወቅ ሁሌም ረጅሙና ፈታኙ መንገድ ምርጫህ ይሁን።

   በረጅም ድካም የማይገኝ ነገር የለምና

          ውብ የስኬት ጊዜ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

💎አንተ ከነሱ የተለየህ በመሆንህ ሲስቁብህ አንተ ደግሞ አንዳይነት በመሆናቸው ሳቅባቸው!

ንስር የጨለመውን ወጀብ ሰንጥቆ ያልፋል እንጅ ጨለማው እስኪያልፍ አይጠብቅምና ጀግናም ጥዋት በወጣበት ስታይል አይመለስም ለማለት ነው ። 😉

አለም ለደፋሮች ታደላለች። ወደ ከፍ ያለ ማንነት ጉዞ ስትጀምር የነፍስክ ጥንካሬ ተአምራዊ ወደ ሆነ ቦታ ያደርሥሀል።

ሽብርቅርቅ ያለች ቅዳሜ ትሁንልን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

❤️ነፍሴ ስትመክረኝ …

የውስጥ ሰላም ከብር ፣ ከወርቅ ፣ ከአልማዝም ሆነ እንቁ ይልቃል ፤ ስኬታማነት ከውስጥ ሰላም ፣ ደስታና ፍቅር በጥብቅ የተቆራኘ ካልሆነ ትርጉሙ ጎዶሎ ነው። ወደ ሀቅ የምትጠራህ ነፍስህን በድለህ ሺህ ግዜ የምድር ሃብት ብትሰበስብ ሀብትም ሆነ ሌላ ነገርህ የውስጥ ሰላም እስካላስገኘልህ ድረስ ተሳካልህ ተብሎ አይታመንም ፤  በዚህ መልኩ የምታገኘው ነገር " ይዘህ ተገኘህ " እንጂ ተሳካልህ አያሰኝም።.

📍ሰላም የሚያሳጡ ፍጡራኖችን ያየህ እንደሆነ በሌሎች ሰዎች ዋጋና መስዋትነት ማትረፍ የለመዱ ፤ ከራሳቸው ጋር ሰላም መፍጠር ያልቻሉ ስግብግቦች እንደሆኑ  ለሰከንድ አትጠራጠር። ከእንደዚህ ዓይነት ስግብግብነት ተጠቆጠብ የሰላም እሴትህን ጠብቅ ፣ ይዘው የተገኙት እየቀደሙህ እየመሰለህ የመልካምነት ጉዞህ መሐል ላይ አትወዛገብ ከመልካምነት እና ከሀቅ በላይ አድካሚና አሸልቺ ግን ደግሞ ፍሬው ጣፋጭ የሆነ እፁብ ድንቅ መታደልና መባረክ የለም።

💡አንዳንድ ጊዜ በራስህ ዓለም ዉስጥ ብቻ ለመኖር ሞክር፡፡፡ ወደ ምድር የመጣኸው ትርጉም ላለው ዓላማ ነውና ሁሉም ቦታ ላይ ጥቀም፡፡ በደረስክበት ቦታ ሀሉ መልካም ዝራ፡፡

📍እቅድህን በመኖር ሂደት በሚገጥሙህ ፈተናዎች አታማር ከአሁን ቀደም የሆኑ ፣ እየሆኑ ያሉ ፣ ከአሁን በሁዋላ በፈለግከውም ሆነ ባልፈለግከው መንገድ የሚሆኑ ነገሮች ሁሉ በምክንያት ያጋጠሙህ እንደሆኑ እመን። የፈተና መብዛቱ ለበጎ ነው፡፡ አካሄድህን እንድታስተካክል ይረዳሃል፡፡ በችግሮች ዙሪያ ተጠበብ እንጂ አትጨነቅ ፤ ለመልካምነትና ከሀቅ ጋር ለመታረቅ የረፈደ የሚባል ግዜ የለም ፤ የቻልከዉን ያህል ስራና እረፍ ፤ ቀሪውን ለፈጠረህ ጌታ ተወው።

ሀቀኝነትን ድፈር ፤ ሀሜተኝነትንና ዋሾነትን ፍራ

💡ደፋር ይሰማል ፣ ያደምጣል ፣ ይናገራል ፣ ይመረምራል ፣ ይፅፋል ፣ ይወስናል ፤ የሰማውን ሁሉ እንደ ሰነፎችና ፈሪዎች እውነት ብሎ አያምንምም አይፈርጅምም ፤ የሰማኸውን ሁሉ እንደ እውነት አምነህ ደግመህ ደጋግመህ ሳታረጋግጥ አታውራ ፤ ማጣራትን አስቀድም ፤ ሳትጠይቅ እና ሳታመዛዝን አትፍረድ።

ስምህን ከምታውቀው በላይ እርግጠኛ ሁን

💡እንዲህ ስታደርግ ሁሉም የሚታየው ጭለማ ፣ የሚያወራው ስለጭለማ ቢሆን ላንተ የሚታይህ ብርሃን እንጂ ሌላ አይሆንም። አትጠራጠር ንስር አሞራ ፈተናዎቿን ከደመናው በላይ ከፍ በማለት እንደምትሻገረው አንተም ፈተናዎችን ከችግሮች በላይ ከፍ ብለህ በማለፍ የውስጥ ሰላምህን ቀጣይነት እያረጋገጥክ ማሳካት ወደ ምትፈልገው ግብ የማትደርስበት ቅንጣት ታክል ምክንያት አይኖርም።

📍እናም እየነዳን ወዳጆቼ

ሁሉንም ነገር በንቃት እየታዘብን እስከነዳን ድረስ  ፤ በችግር ውስጥ ሆኖ በመሳቅ ፣ በደስታ እና በውስጥ ሰላማችን እስካልተደራደርን ድረስ የማንሻገረው ፈተናና የማናሳካው  ግብ አይኖርም።

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

#ምክር ለወዳጅ

📍ወዳጄ ሆይ !

ያወቅከው እውቀት ቢመስጥህ የመጨረሻ እውቀት አይደለም ። በገዛ ድምፁ ባብቶ የሚያለቅስ እንዳለ ሁሉ ያወቀውም እውቀት ሲያስቀውና ሌላውን ሲያስንቀው የሚውል ሞኝ አለ ። የሞትከው ትምህርት ያቆምክ ቀን ነው ። በዓይኖችህ የምታየው ወዳጅህን በጆሮህ አትመዝነው ። ስለ ወዳጅህ ሐሜትን ይዘህ አትምጣ ፣ የሰማህበት ቦታ መልስ ስጥ ። የወዳጅ ልኩ ለወዳጅ ጠበቃ መሆን ነውና ። ደጋጎች ባይኖሩ ዓለም እንደ ቆሰለች ትቀር ነበር ። አንተም በደግነትህ የዓለምን ቍስል አድርቅ ።ማፍቀርህን እንደ ውለታ አትቍጠረው ፣ እውነተኛ ሰው ሌላውን ከመውደድ ውጭ ምንም አማራጭ የለውምና ።

📍ወዳጄ ሆይ !

ዛሬ ያበሳጨህን ነገር በትዕግሥት አሳድረው ። ከቻልህ አሠልሰው ። በልኩ ማየት ትጀምራለህ ። ፈጥነህ መልስ መስጠት ጸጸትን ፣ ተስፋ መስጠትም ቁጭትን ያመጣል ። ፈጣን ፍርድ በሚሰጥባቸው አገራት የተፈረደባቸው በሞቱ በማግሥቱ ንጹሕ ነበሩ ይባላል ።

ወዳጄ ሆይ

የጥንት እውቀት በመደበቅ ፣ የዛሬ እውቀት ግን በመስጠት ይከብራል ። በዚህ ዘመን እውቀትን ብትደብቅ አላዋቂ ትሆናለህ ። የእውቀት ስስት የጠፋበት ዘመን በመሆኑ ልናደንቅ ይገባናል ። የምትወደው ሰው ጋር ለመኖር በዝግ ልብ ሁነህ አትቅረበው ። ብዙ አለመጠበቅ ፣ ይቅር ማለትና ማለፍ እንዲሁም ጠባዩንና የአስተዳደግ ተጽእኖውን መረዳት ይገባሃል ። የምትወዳቸው አንተን የማወቅ መብታቸውን ከከለከልካቸው ይጠሉሃል ። በዝግ በር እንደማይገባ ዝግ በሆነ ልብም ወዳጅ አይስተናገድም ።

💡ወዳጄ ሆይ !

ተዘቅዝቀህ ስታይ ሁሉም ሰው የተዘቀዘቀ ይመስልሃል ። ስትወድቅ ሁሉም ሰው ውዳቂ ይመስልሃል ፣ ስትረክስም የሰው ሁሉ ርኩሰት ይታይሃል ። በእግርህ ቆመህ በጭንቅላትህ አስብ ። በእግር መቆም ባመኑበት መጽናት ፣ በጭንቅላት ማሰብ ማስተዋል ነው ።

📍ወዳጄ ሆይ !

ገንዘብህን ይውሰዱብህ እንጂ አመልህን እንዲወስዱብህ አትፍቀድላቸው ። ስምህን ባገኙት ጭቃ ሊያቆሽሹት ይችላሉ ፣ አንተነትህን ግን አንተ ብቻ ትለውጠዋለህ ። ከሰረቁህ ይልቅ የምትጥለው እንዳይበዛ ተጠንቀቅ ።

💡ወዳጄ ሆይ !

በወንድምህ እጅ ያለውን ክብር ለእኔ ቢሆን ብለህ አትናፍቅ ። ምኞት ምቀኛ ፣ ምቀኝነትም ክፉ እይታ ፣ ክፉ እይታም ነፍሰ ገዳይ ያደርጉሃልና ።  ዕድሜህ እንዳያጥር ትልቅ አዋራጅ አትሁን ። መኖርህ ለሚያስደስታቸው ቅድሚያ ስጥ ። ለሚጸልዩልህ ምርኮህን አካፍላቸው ። ያልተቀበረ ሬሳ እየገደለህ ይመጣል ። ያልተሻረ ቂምም እየመረዘህ ይመጣል ።

ወዳጄ ሆይ !

ተቃውሞን ከፈራህ ሥራ አትጀምር ። ነቀፋን ከሰጋህ ከቤትህ አትውጣ ። ውግረትን ካልጠበቅህ ባለ ራእይ አትሁን ። ለማግኘት ማጣት ፣ ለመክበር መዋረድ አስፈላጊ ነው ። ጸጋ ፈጣሪ የሚበዛልህ በሁለት ነገሮች ነው ። የመጀመሪያው በትሕትና ፣ ሁለተኛው በባለጌዎች በመሰደብ ነው ።

📍እናም ወዳጄ !

ጥቅም ለማግኘት ብለህ የተዋጋኸው ውጊያ በመጨረሻ ባለጠጋ እንጂ ባለ ኒሻን አያደርግህም ። ከገንዘብ ክብር እንደሚበልጥ ተረዳ ። የረዳህን ፈጣሪ አልሰጠኝም ብሎ ማማት ነውና እያለህ ከሌላቸው ጋር አትሻማ፣ የሌለህን ስትመኝ ያለህን እንደምታጣ ተገንዘብ ። ግማሽ ደግነት የክፋት ያህል ነውና ለጉዳይህ ብለህ ቸር አትሁን ። የጎደለ እንስራና ባዶ አዳራሽ ድምፅ ያበዛሉና በእውቀትና በመንፈስ ሙሉ ሁን ።         

  ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

📍ወዳጄ ሆይ

አትድከም፣ አትዘን ማን ያውቃል ሸክምህና ህመምህ ሁሉ ተራግፎ ሌላ ሰው ሆነህ ትነሳ ይሆናል። ያለን ፈጣሪ እንኳን በአንድ ሙሉ ሌሊት፣ በቅጽበት ጊዜ ዉስጥም ብዙ ተዓምር ይሠራል።

በቀልባቸው ንፅህና ብቻ ሰላማቸው የበዛ ሰዎች አሉ። ቀልባችሁ ንፁህ ሲሆን ሰላማችሁ ይበዛል፣  ለሌሎች መልካም ስትመኙ በረከታችሁ ይሰፋል። ልብህ የተጠራጠረዉን ነገር ተው፤ ልብ ከዐይን በላይ ያያልና።ወደ ፊት የሚሆነውን ሳትበሳጭ ሳትሰለች በትግስት ጠብቅ።የማይረባና ጥቅም የሌለው ነገር በመከተል ጉልበትህን አታባክን።

ወዳጄ ሆይ

ከሐዘን በኋላ ደስታ እንጂ ምን አለ!
ማጣትን ማግኘት እንጂ ሌላ ምን ይከተለዋል! ምሽቱስ እየነጋ አይደል የሚሄደው?? ከጨለማ በኋላ ብርሃን እንጂ ምን ይመጣል፡፡ የጨለመው ይበራል ፣ የጠፋዉም ይገኛል ።

ሕይወትህን መስዋዕት ያደረግህለት ሥራህ በፈረሰና በተናደ ጊዜ ይህንን ክፋ ፈተና ተቀብለህ ተስፋ ሳትቆርጥ የጠፋውን ሁሉ መልሰህ ለማቋቋም በደከመ መሣሪያ ለመሥራት ሳታመነታ ተነሣ።ያለነው የፈተና ምድር ውስጥ ነው። በበሽታ መፈተን አለ። በኀጢአት መፈተን አለ። በዕዳ መፈተን አለ ፣ የምድር ፈተናዎቿ ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም።

እናም ወዳጄ

ያለህን የሌለህን ገንዘብህን ሁሉ አንድነት አከማችተህ ስትሰራበት ሁሉንም ባንድ ጊዜ ስትከሥር አጣሁ ከሠርኩ ብለህ ቃል ሳትተነፍስ አሁንም ሰርተህ ለማተረፍ ከሥር ጀምረህ እንደ ገና አንድ ብለህ ድከም። ዐሳብህ ጉልበትህ ሥሮችህ ታክቶዋቸው በደከሙ ጊዜ ልብህ ብቻ ይበርታ።

ንፋስ የማይወዘዉዘው ዛፍ የለም። ሀሳብ ወስዶ የማይመልሰው ሰዉም የለም። እንዲህም ሆኖ የማይወድቅ ዛፍ አለ። በፈተና የሚፀና የሚበረታ ሰዉም አለ።

            ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

⚡️የጨረቃዋን ውበት የሚሻ ጨለማውን አይሸሽም፣ ጽጌረዳዋን ብሎ የሄደ እሾሁን ፈርቶ አይመለስም
ፍቅርን ከልቡ የሚፈልግ ሰው ከራሱ አይደበቅም ፣እራሱን ፈጽሞ አይሸሽም ።

የምንፈራው ነገር ብዙ ጊዜ የምንመኘውና የሚበጀንን ነገር ነው። ሰዎች ከእውነተኛ ፍላጎታችን የመሸሽ ባህሪ አለን። በምክንያቶች እራሳችንን እያታለንን፤ ሊነቃ የሚታገለውን ድብቅ ምኞታችንን መልሰን እናስተኛዋለን።

✨ፍርሃታችንን ብንከታተለው..ጥበባችንንም እዛው ማግኘታችን አይቀም። ለዚህም ነው ልትገባበት የምትፈራው ዋሻ ውስጥ ነው ሀብትህን የምታገኘው የሚባለው። ውብ ነገሮችን ለማግኘት ሰው ፍርሃቱን አልፎ መሄድ አለበት፤ በምንፈግልጋቸው ነገሮችና በእኛ መካከል የቆመው ትልቁ ግድግዳ ካለማውቅ የሚመነጨው ፍርሃት ነው:: ጨለማውን የደፈረ ጨረቃን፤ እሾሁን ያልፈራ ጽጌረዳዋን፤ እራሱን ያወቀ ፍቅርን ማግኘቱ አይቀርም::

🔑ፍርሃታችንን....እንከተለው ፤ የፍርሃት ዱካ እውነትኛ ምኞታችንን ያሳይን ይሆናል። ያንቀላፋውን ምኞት የሚቀሰቅሰውም ይኸው ለፍርሃት የምንሰጠው ምላሽ ብቻ ነው።

             ውብ አሁን♥️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

እነዚህ መፅሐፎች ቅፆች ያሉት ሰው የሚሸጥ ካለ እንደው ወይም የምታውቁት ሰው ካለ ብትተባበሩኝ

@Nagayta በዚህ ሊንክ ልታገኙኝ ትችላላችሁ

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

✨የጥበብ ምሽት

ማህበረሰብ አንቂው እና ወግ አዋቂው።

🔊አቶ በሀይሉ ገብረመድህን


ውብ ምሽት♥️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🛑እያንዳንዳችን ፍቅርን የምንገልጽበት የራሳችን የሆነ መንገድ አለን። እናትና አባት ለልጆቻቸው፤ ወንድም ለእህቱ፤ እህት ለወንድሟ፤ ጓደኛ ለጓደኛ፤ ሚስት ለባሏ፤ ባል ለሚስቱ፤ ፍቅራቸውን በተለያየ መጠንና መንገድ ይገልጹታል። በፍቅር ስም ብዙ ስህተቶች ሲፈጸሙ ይስተዋላል። ፍቅር ስህተት ሆኖ ሳይሆን የሚገለጽበት መንገድ ልክ ስላልሆነ ብቻ። ምክንያቱም ፍቅር ምን ጊዜም በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ስህተት ሆኖ አያውቅም።

🔷ፍቅር ጉዳት የሚሆነው፤ ስህተት የሚመስለው የሰዎችን ልብ የሚሰብረው፤ ፍቅር ስህተት ሆኖ ሳይሆን ያስተላላፊው ስህተት ሲኖር ነው። ፍቅር ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ለመተላለፍ ነጻነትን ይፈልጋል። ነጻነትን የተነፈገ ፍቅር ለተቀባዩ እዳ ይሆናል። ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ አለቅጥ ሲቆጣጠሩ በልጅ እና በወላጅ መካከል ያለው የግልጽነት ድልድይ ይሰበራል። ወላጅ ፍቅሩን “እኔ
አውቅልሃለው” በሚል አገላለጽ ሲገልጽ ልጆች በወላጅ ተጽዕኖ ነጻነታቸውን መስዋት ያደርጋሉ።

♦️ ይህ ማለት ወላጆች ልጆቻቸውን መቆጣጠር የለባቸውም ሳይሆን ፤ እስከምን ደረስ መሆነ እንዳለበት ልብ ሊባል ይገባል። ወላጆቻቸውን ፍራቻ ልጆች ብዙ ስህተቶችን ይፈጽማሉ ። ውድቀታቸውን እና የህይወት ፈተናዎቻቸውን ለወላጆቻው መግለጽ የሚከብዳቸው፤ ወላጆች ፍቅራቸውን የገለጹበት መንገድ ልክ ባለመሆኑ ነው። በተለይ በኛ ማህበረሰብ ግልጽነት የሚጎድለን ፤ ወላጆቻችን ፍቅር አንሷቸው ሳይሆን አገላለጻቸው ወደ ፍርሃት ስለሚወስደን ነው።

🔷በየትኛውም ቦታ እና ግንኙነት ፍቅር ህይወት ሊዘራ የሚችለው ነጻነት ስኖረው
ብቻ ነውና ፣ የምንወደውን ጽጌሬዳ ቆርጠን ቤት አናስቀምጠው ምክንያቱም ይሞታልና። ይልቁንም እውነተኛ ፍቅር ካለን ባለበት እንዲያብብ እንፈቅድለታለን። የምወዳቸውን ሰዎችም ማስተናገድ ያለብን እንዲህ ነው፤ እውነት የምንወዳቸው ከሆነ ነጻነታቸውን እንስጣቸው። በፍቅር ስም እነሱ የመረጡትን ሳይሆን እኛ የመረጥልናቸውን እንዲኖሩ አናስገድዳቸው።

📍በዚህም ምድር ላይ ለሰው ከነጻነት የበለጠ ስጦታ የለም። በነጻነት ውስጥ እምነት አለ በራሷ እንደትበር የተለቀቀች ወፍ ሌሎች በሷ እንደሚያምኑ ይሰማታል። በነጻነት ውስጥ ግልጽነት አለ፤ የሚሸፈን የሚከደን ምንም ነገር ስለሌለ። ፍቅር ደግሞ ያለእመነት እና ግልጽነት ዋጋ አይኖረውም። ለዚህ ነው ፍቅር እና ነጻነት ተለያይተው መሄድ የማይችሉት።

የምንወዳቸውን ሰዎች እናስብ ፍቅራችንን እንዴት እየገለጽንላቸው ነው? ነጻነታቸውን በሚጋፋ መልኩ ከሆነ እስቲ ትንሽ ቆም ብለን እናስብበት⁉️

           ውብ  አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

♦️ምክር ለወዳጅ

📍ወዳጄ ሆይ !

አዲስ ግኝት የመሰለህ እውቀት ከራስህ የመነጨ ሳይሆን ፈጣሪ ከሰጠህ አእምሮና አብርሆት የተገኘ ነው ። እውቀትን የጣለ እምነት ፣ እምነትን የጣለ እውቀት አይኑርህ ። እውቀት የሌለው እምነት ራስን ማደንቆር ነው ። የሚታወቅ ነገር ሳለ ፣ ማወቂያ መሣሪያው አእምሮ ከተሰጠህ የማወቅ ግዳጅ አለብህ ። ሰውን ሰው የሚያደርገው በእውቀት የተፈጠረና በእውቀት የሚያድግ መሆኑ ነው ። እምነት የሌለው እውቀት ግን ማለስለሻ እንደሌለው ተሽከርካሪ እርስ በርሱ የሚፋጭ ፣ ድምፁ የሚረብሽ ፣ ዕድሜው የሚያጥር ነው ።

📍ወዳጄ ሆይ !

እኔ እንጂ እነርሱ ምን አለባቸው ? አትበል ። ብዙ ባለበት ዓለም ምንም የሌለበት ፍጡር የለም ። ሕፃናትም በረሀብ ፣ ልጆችም በበሽታ ይሰቃያሉ ። እንስሳትም በሰው የመጣውን ሐሣር ይካፈላሉ ። አንተ ስላለህ ሁሉ ያለው አይምሰልህ ። አንተ ስላጣህም ሁሉ ያጣ ሁኖ አይሰማህ  ፣ ብርታት ሌላውን ከማበርታት ይገኛል ። ሌላውን ስታበረታ አንተም በርትተህ ትገኛለህ ።

📍ወዳጄ ሆይ

ሰዎችን የምታሸንፋቸው በፍቅር ፣ የሚያሸንፉህ በክብር ነው ። እውነተኛ ፍቅር መስጠት ካልቻልህ በሽንገላ ራስህን ማድከም ፣ ትዝብት ላይ መውደቅ አያስፈልግህም። የጎላ ታይታ መውደድ ወደ ብዙ መሰወር ይለወጣል ። “እዩኝ ፣ እዩኝ ያለ ገላ ፣ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል” እንዲሉ ፣ ጓዳህን ለሁሉ አታሳይ፣ ምሥጢርህን በአደባባይ አትግለጥ። ክብር በትግል አይገኝም ፣ መፈራትም እውነተኛ ክብርን አያመጣም።

📍ወዳጄ ሆይ

ከፍታህን ከፍ ባለ ቃል ሳይሆን ከፍ ባለ ኑሮ ግለጠው። ሕያው መንፈስ አለህና በቁሳቁስ አትመካ፣ የሰው ንብረት አትቀማ! ሰውን ወልዶና ተዋልዶ ኑሮውን ከመሰረተበት መሬት አትንቀል፤ አታፈናቅል። እንጀራው ለሁሉ እንዲበቃ አድርገህ አስፋው! ለዚህ ፍቅር ያስፈልግሃል ፣ ይህ የሚቻለው ፍቅር ሲኖር ብቻ ነውና፣ ልብህ ለሰው ልጅ ሁሉ በፍቅር እንዲሞላ ይሁን።

📍ወዳጄ ሆይ

የሆነው መሆን ስላለበት ነው ። ፍርሃት የታዘዘን ነገር ከመምጣት አያድነውም ። በፈቃድህ ወደ እዚህች ዓለም ምንም ነገር አላመጣህምና ፣ እንዴት ይህ ይደርስብኛል? አትበል። የቀለጠ ወርቅ ጌጣጌጥ እንደሚይሆን የተጠረበ ድንጋይ ሐውልት እንደሚይሆን ሁሉ ፣ እንተም በብዙ ችግሮች ውጣ ውረዶች ባለፍክ ቁጥር አንተነትህ እያደገ መሆኑን አትርሳ !

🔺ታዲያ ወዳጄ፦

ቅን ልብ የጨለማ ዘመን መብራት ነውና ቅንነት ይኑርህ ። ማስተዋል የሌለበትን ዓይናማነትን አትውደደው ። ሰውን በፍቅር እንጂ በኃይል አትሳበው ፣ የሚያደምጡህን አድምጣቸው ። ራስህ የሠራኸውን ራስህ እንዳታፈርሰው ሥራህን በችኩልነት አትፈጽም ፣ ትዕግሥት የጎደለው ቤት በተገነባ ቁጥር መፍረሱ ይፈጥናል ። የረዳሃቸው ሌሎችን ሲረዱ ለማየት ናፍቆት ይደርብህ፣ የሰው ሰውነቱ መታያው ልቡናው ዉስጥ በሰነቀው ቅንነት ነውና፣ በሽተኛን ከሚፈውስ ባለ ስጦታ ፣ የተከዘን ልብ የሚያጽናና ወዳጅ ይበልጣል።

               ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

📍ደፋር መሆን ይኖርብናል ያልተሄደበትን መንገድ ለመሄድ መድፈር

ትእቢትን እልህን ጥላቻን ይሉኝታን ለመተው መድፈር

ራስን ለማዳመጥ መድፈር

💡አዎ ብዙ በደል ፈፅመሀል ተፈፅሞብሀል። ብዙ ሰው ጠልተሀል፣ ተጣልተሀል ፣  ተጠልትሀል ፣ ልብህ ተሰብሯል፣ ልቦችን ሰብርሀል ፣ግን ደግሞ ከዚህ ሁሉ ጋር ታርቀህና ራስህን አስታርቀህ ዳግም ለመውደድ ፣ ዳግም ለማዘን ፣ዳግም ለመርዳት፣ ዳግም እርዳታ ለመጠየቅና በቅንነትና በፍቅር ለመኖር ድፈር።

📍መጀመርያ ግን ከራስህ ጋር ለመታረቅ ድፈር። ራስህን ከነሙሉ ስህተቶቹ፣ ግድፈቶቹ ፣እንከኖቹ፣ውሸቶቹ፣ ቅጥፈቶቹ፣ አስመሳይነቶቹ ሁሉ ለመቀበል ለማዳመጥና ለመውደድ ድፈር

የፍቅር የይቅርታ ዘመን ነው ሲባል ወደሰማይ አታንጋጥ፣ ወደጎረቤቶችህና ጠላቶቸ ብለህ ወደፈረጅካቸው ሁሉ አታፍጥጥ

መጀመርያ ከራስህ ጋር ለመታረቅ ወደውስጥህ ተመልከት፣ ወደራስህ ተመለስ ፣ ውስጥህን ፣ልብህን ፣ ህሊናህን አፅዳ፣ሰው የሚሰጥህ ክብር አንተ ለራስህ በምትሰጠው ሚዛንና መጠን ነውና ለራስህ ትልቅ ዋጋና ብዙ ክብር ይኑርህ

💡ራስን መመልከት ራስን ወደ መሆን የሚያደርስ ወሳኝ መንገድ ነው። ራስህን ስትመለከት የወንድምህን ጉድፍ ሳይሆን የአንተን ተራራ ታስተውላለህ፥ በዚህ ውስጥ ደግሞ ተራራህን እየነቀልክ ራስን ወደ መሆን ታድጋለህ። ራስህን ስትሆን ብዙ ነገሮችን ታሸንፋለህ፥ መሰናክሎችን በቀላሉ አልፈህ፥ የነከሰህን የመከራ ጥርስ ውሃ የማድረግን ጥበብ ትጎናጸፋለህ።

🔑ብቻ ምን አደከመህ ራስህን ስትሆን ብዙ የደረብካቸው አላስፈላጊ ኮተቶችን ከራስህ ላይ አውርደህ፥ ንጹህ አንተነትህን ብቻ ያነገበ ማንነት ስትገነባ ያን ጊዜ ሰው መሆን ትጀምራለህ።እናም ራስህን ለመውደድ ድፈር።

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍@EthioHumanitybot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🛑 ኢኮኖሚክስ ላይ 'Water & Diamond paradox' የሚባል እሳቤ አለ... ለኑረት ወሳኙ ነገር ውሃ ነው ፣ ግን 'እርካሽ' ነው። አልማዝ ለህላዌ የሚያበረክተው ድንቡሎ የለም  ግን ውድ ነው። ለዚህም ይመስላል አንስታይን "The important things are always simple" ማለቱ...

ዘግይቶም ቢሆን የሚገባህ እውነት ነገሮችን በውድና ርካሽ የሚፈርጀው አስተሳሰብ እንጂ የነገሩ ወሳኝነት አለመሆኑ ነው። እርግጥ ማሕበረሰባዊ ስምምነቶች ለተፈጥሮ ህግ ከመገዛት ይልቅ መንጋነትን ያበረታሉ።

ለምሳሌ፦
፨ ዋናው ቁምነገር አብሮነትና ፍቅሩ ቢሆንም ውዱ ግን ሰርጋችን ነው...
፨ ትልቁ እውቀት ራስን ማወቅ ቢሆንም ውዱ ግን ከአስኳላ የምንገዛው ነው።
፨ ጠቃሚው ውበት ጸጥታ ቢሆንም የምንከፍለው ግን ለሚበጠብጠን ጩኸት ነው።
፨ ጤናችን ያለው ንጹህ ውሃ ውስጥ ቢሆንም ብዙ የምንከፍለው ግን ለመታመሚያችን አልኮል ነው... ወዘተ

እልፍ ርቀት ሮጠህ ስታበቃ ቆም ብለህ 'ለዚህ ጉዳይ ይህን ያህል ዋጋ መክፈል ነበረብኝን?' ብለህ ብትጠይቅም መሮጥህን ግን አታቆምም።

በዙሪያህ ያሉ ነገሮች ጡዘትህን እንጂ ቆምታህን አያበረቱም ፣ ይልቁን በውድድር ውስጥ እንድትቆይ ይገፉሃል ከጓደኛህ ትወዳደራለህ ፣ ከጎረቤትህ ትወዳደራለህ፣ከባልደረባህ ትወዳደራለህ ፣ ከንግድ አቻዎችህ ትወዳደራለህ... እናም በምስሉ ላይ እንደምታየው ማቆሚያ በሌለው ዙረት [Vicious circle] ውስጥ ትቧችራለህ።

📍ዛሬ የሆነ ነገር ለማግኘት ትሮጣለህ... ደርሰህ ስትይዘው ይቀልብሃል፣ነገ ሌላ ለመጨበጥ ትዘረጋለህ፣ ደርሰህ ስታየው 'ለዚህ ነው በሬዬን ያረድኩት?' ያስብልሃል... እንደገና ሌላ ሩጫ. እንደገና ሌላ ፍለጋ... እንደገና ሌላ መባከን...

እጅህ ላይ ያለው ካላስደሰተህ እርግጠኛ ሁን ሊመጣ ያለውም አያረካህም። በበርህ አበባ ሳትፈነድቅ በገነት ውበት አትመሰጥም። ደስታን ከውጭ ከመፈለግ በላይ ጉድለት የሚመስለኝ ይህ ነው። እየፈለጉ መቀጠልን ማቆም ባይቻል በደረሱበት አለመብቃቃት ትልቅ ጉዳት ነው የደረስክበት ደግሞ 'አሁን' ነው ይህ ቅጽበት.አሁንና እዚህ።

አንድ ጊዜ የምረቃዬ መጽሔት ላይ ከፎቶ ስር ለሚሰፍር ጽሑፍ 'የእኔ ቀን ነገ ናት' የሚል ቃል ሰጥቼ ነበር... አሁን ላይ ቆም ብዬ ሳስብ 'ምን ሆኜ ነው ግን' እላለሁ. እንዴት ሰው እርግጠኛ ከሚሆንበት ዛሬ ይልቅ በማያውቀው ነገ ላይ የደስታውን ውበት ያንጠለጥላል?  ደስታ ኑረትን ግድ ይላል እኮ... 'ነገ እንትን ሳገኝ እደሰታለሁ' የምትል ከሆነ ለመደሰት ቀጠሮ እየሰጠህ ነው፣ ከዚያም በላይ ደስታህን በነገሩ መኖር አለመኖር ላይ እየመሰረትክ፣

ደግሞስ 'ለደስታ ምን ያህል ነው የሚበቃን?' ስንት ብር? ስንት መኪና? ምን ያህል ቁስ?

በዙሪያዬ ብዙ 'ያላቸው' - ተነጫናጮች እና ደግሞ 'ምንም የሌላቸው' ደስተኞች አየሁ ፣ ብዙ ሃብታም የበሽታ ቋቶችና ድሃ ፍልቅልቅ ፊቶችን ሳስተውልም ይሄ ጥያቄ ትዝ ይለኛል፦
.
.
መልሱ እኮ በአጭሩ "ደስታ ውስጣዊ እንጂ ቁሳዊ [ሰበባዊ] አይደለም" የሚለው ነው። ሆኖም በተግባባንበት መንገድ ሄጄ 'ለመደሰት ስንት ያስፈልገናል?' እላለሁ ፦ ምንም አይበቃንም!!* ምናልባት ምድርን የሚያህል ሃብት ቢኖረን እንኳ ሌላ ፕላኔት ማሰሳችን አይቀርም፣ ደስታ ግን ከብዛትም ሆነ ከነገር ጋር አትቆራኝም።

አዎን... ደስተኛ መሆን ካሻህ ባለህ ተብቃቃ Be Content እልሃለሁ!!

📍'የሰው ልጅ ፍላጎት ገደብ የለውም' በሚል ከንቱ ስብከት እየተነዱ 'ያለኝ ይበቃኛል' ማለት እንደሚከብድ ግልጽ ነው።ያም ሆኖ በፍላጎታችን ላይ የምንሰለጥን እንጂ ፍላጎት የሚሰለጥንብን እንዳልሆንን ማወቅም ጠቃሚ ይመስለኛል። አግበስባሽነት በማግኘት ላይ እንድትመሰጥ እንጂ ባለህ ደስታ እንድትፈጥር ፣ አሁን ያለህን ሐይወት እንድታጣጥም ዕድል አይሰጥምና።       

                     ✍ደምስ ሰይፉ
                  @BridgeThoughts
    

            ውብ አሁን ❤️

@Ethiohumanity
@EthioHumanity

@EthiohumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

📍አንዳንዴ ምን ሆነሀል ስትባል የማትመልሰው ብዙ መሆን አለ። ለመናገር የማይመች ለመተው የማይቀል ብዙ ስሜት አለ ..ለአንተ የከበደ ለሌላው የቀለለ ነገር አለ ።

💡እንዴ ይሄ እኮ ቀላል ነው ይሄ እኮ አያስጨንቅም በሚባል ቃል የሚሸነፍ ለአንተ/አንቺ ግን የከበደ ስሜት አለ ።
ምን ሆነሀል ስትባል ምንም ብለክ የምታልፈው ውስጥህ ብቻ የምታንሸራሽረው እያዳመጥክ የምትታመምበት ። ከባድ ስሜት አለ ከባድ.......

❤️ምናልባት የምትፈልገው ስፍራ ላይ አልተቀመጥክ ወይንም የምትመኘውን ነገር አላገኘህ ይሆናል፣ ቢሆንም ተስፋ አትቁረጥ ፣ ተስፋ የመኖር ምክንያት ነውና፣

እየኖርን ነው አይደል? በሰው ሳይሆን በፈጣሪ!!
ትላንት የኖርነው ህይወት በነበር ይተካል፣
ሰዎችም ኖረው ነበሩ ይባላሉ፣
ፈጣሪን ግን ነበር ብለን አናወራውም ፤ ያለና የሚኖር ፣ በዛሬያችን ,በነጋችን አልፎም በዘላለም ውስጥ ኗሪ ነው ።
" የትላንት ነበሮቻችን በእሱ መኖር ተረስተዋል"

እናም ወዳጄ

አትድከም ፣ አትዘን ። ማንያውቃል ሸክምህ ህመምህ ሁሉ ተራግፎ ሌላ ሰው ሆነህ ትነሳ ይሆናል። ያለን ፈጣሪ እንኳን በአንድ ሙሉ ቀንና ሌሊት፣ በቅጽበት ጊዜ ዉስጥም ብዙ ተዓምር ይሠራል።

💡ንፋስ የማይወዘዉዘው ዛፍ የለም። ችግር ፣ ፈተና ፣ ሀሳብ ወስዶ የማይመልሰው ሰዉም የለም። እንዲህም ሆኖ የማይወድቅ ዛፍ አለ። በፈተና የሚፀና የሚበረታ ሰዉም አለ። ዐሳብህ ጉልበትህ ሥሮችህ ታክቶዋቸው በደከሙ ጊዜ ልብህ ብቻ ፈጣሪን ይዞ ይበርታ።

          ውብ ምሽት❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

📍‹‹በቂ›› ስንት ነው? (How much is enough!

🔷ጊዜ በቂ አይደለም፡፡ ሕይወት በቂ አይደለም፡፡ ዕውቀት በቂ አይደለም፡፡ ገንዘብ በቂ አይደለም፡፡ ደስታችንም በቂ የሚባል ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡  ወዳጅነትም ሆነ ዝምድና በቂ ነው አይባልም፡፡ የዚህ ዓለም ፍቅርም በቂ አይደለም፡፡ አብዛኛው የዘንድሮ ወዳጅነትም ሆነ ዝምድና በወረት ያጠረ እንጂ ዘላቂ አይደለም፡፡

🔶‹‹በቂ›› የሚለውን ቃል በሁለት ፊደል ብቻ መወከል ፍትሐዊ አይደለም፡፡ በቂ እንደየሰዉ መስፈሪያ ከፍም ዝቅም ይላል እንጂ እቅጩን ሆኖ አያውቅም፡፡ የምንም ነገርን መስፈሪያ በግምትና በስምምነት ወይም ከዚህ እስከዚህ የምንለው እንጂ በራሱ በቂ የሆነ አይደለም፡፡ በቂ የመጠን ጉዳይ ነው፡፡ መጠንን መመጠን ደግሞ የመጣኙ ፋንታ ነው፡፡ አንዱ ከመጠኑ አስበልጦ አሙልቶ ሲያፈሰው ሌላው ደግሞ ከመጠኑ በታች አድርጎ ያጎድለዋል፡፡ በቂን የሚያበቃው በአዕምሮ የበቃው ብቻ ነው፡፡

♦️ኑሮ ያልበቃን፣ ገንዘብ ያልበቃን፣ ዕውቀት ያልበቃን፣ ደግነት ያልበቃን፣ ፍቅር ያልበቃን የምንፈልገውን የእውነት ስለፈለግነው ሳይሆን ሌሎች ስለፈለጉት ብቻ እኛም ሰለፈለግነው ነው፡፡ አዎ ብዙዎቻችን የምንፈልገውን የማናውቀው ፍላጎታችን የተመሰረተው በሌሎች ፍላጎት ላይ በመሆኑ ነው፡፡

🔹በእርግጥ መሠረታዊው የሰው ልጅ ፍላጎት ተመሳሳይ ቢሆንም አፈላለጋችንና ፈልገን የምናመጣበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡ የሆድ ጉዳያችን፣ ርሃባችን፣ ጥማችን ስሜቱ የጋራ ቢሆንም መንፈሳዊ ረሃባችንና ጥማታችን፣ እንዲሁም አስተሳሰባችንና ግባችን የተለያየ ነው፡፡ የብቃት መለኪያችንም የሚለየው ‹‹በቂ›› የሚለው መስፈሪያ እንደየአስተሳሰባችን አንድ ወጥ ባለመሆኑ ነው፡፡

ሮበርት ስኪደልስኪ የተባለ ፀሐፊ እንዲህ ይላል፡-
‹‹የምንፈልገው ከመጠን በላይ ስለሆነ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ የምንፈልገው ሌሎች ከሚፈልጉት የበለጠ እንዲሆን ስለምንሻ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሌሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚፈልጉት እኛ ከምንፈልገው በላይ እንዲሆን ነው፡፡ ይሄም መጨረሻ ወደሌለውና አሸናፊው ወደማይለየው ፉክክር ውስጥ ከትቶናል፡

🔶በመጠን ኑሩ!! ከዕውቀት ሁሉ ዕውቀት ፦ መጠንን ማወቅና ‹‹በቂ››ን መገንዘብ ዋነኛ የህይወት ጉዳይ  ነው፡፡ ከመጠን ያነሰም ሆነ የበዛ ጣጣ አለው፡፡ ከበቂ በላይም ሆነ ከበቂ በታች ሁሉቱም አይጠቅሙም፡፡ በቂ መካከለኛው ነጥብ ነው፡፡ በቂ መጠን ነው፤ መጠን ደግሞ ማስተዋል ነው፡፡

🔷ወዳጄ ሆይ የብልፅግና ዋነኛ ግብ መሆን ያለበት እንደገብጋቦች ማከማቸት ሳይሆን ሕይወትን በምድር ላይ በደስታ ማኖር ነው ። አንድ ሰው ሀብታም ነው ሚባለው ደሞ ባለው ነገር ሲረካና በቃኝ ሲያውቅ ብቻ ነው። አንተም መጠንህን እወቅና ብቃትህን ተጎናፀፍ፡፡ የምትፈልገውን ሁሉ ለማሟላት ስትል ዕድሜህን አትጨርስ፡፡ ከምትፈልገው ይልቅ የሚያስፈልግህን ምረጥ፡፡ ማግበስበስን ሳይሆን መመጠንን ልመድ፡፡ የ‹‹በቂ›› መስፈሪያህን በቅተህ አግኘው፡፡

        በቂ ሕይወትን ተመኘን!
           ውብ ቅዳሜ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🔴ብርጭቆህን ባዶ አድርግ!!

ቻይና ውስጥ አንድ በጣም ጠቢብ የዜን ፍልስፍና (Zen Philosophy) መምህር ነበር።  ሰዎች የእርሱን እርዳታ ለማግኘት እና ጥበብ ለመቅሰም  ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ይጓዙ ነበር።  

አንድ ቀን አንድ የተማረ (ምሁር) ምክር ለማግኘት መምህሩን ይጎበኛል።   ምሁሩም ስለ ዜን የህይወት ፍልስፍና ለመማር እንደመጣ ይናገራል።

🔹ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ውይይቱ ተጀመረ። ምሁሩ አእምሮው ‘በሁሉን አውቃለሁ ባይነት’ የተሞላ እና በእራሱ አመለካከት፣ አስተሳሰብ  እና እውቀት ፍፁምነት  ያምን ነበርና በንግግራቸው ወቅት መምህሩ የሚናገረውን እና የሚያስተምረውን ከመስማት እና ትኩረት ከመስጠት ይልቅ የራሱን ታሪክ እና ስለ ምሁርነቱ በማውራት መምህሩን የመናገር እድል ይነሳዋል። 

🔹መምህሩም በእርጋታ አንድ ላይ ሻይ እንዲጠጡ ሐሳብ ያቀርባል። ለእንግዳው (ምሁሩ) ባቀረበው ብርጭቆም ሻይ ይቀዳለታል።  ብርጭቆው ሞላ። 

🔹ነገር ግን መምህሩ እየፈሰሰም ቢሆን ሻይውን መቅዳቱን አላቆመም። ጠረጴዛው ላይ እስኪፈስ ድረስ ሻይ እየቀዳለት ነበር።  ሻይው ወለሉ ላይ ብሎም በምሁሩ ጃኬት ላይም ይፈስ ነበር።   ምሁሩም በመገረም እየተመለከተው ‘’“ተው እንጅ!  ብርጭቆው እኮ ሞልቷል።  ማየት አትችልም እንዴ ” ይላል።

🔸መምህሩ በፈገግታ “ብርጭቆህን ባዶ አድርግ! አንተም  ልክ እንደዚህ ብርጭቆ ሁሉ አእምሮህ ባረጁ ሃሳቦች እና እምነቶች የተሞላ ስለሆነ ከዚህ በላይ ምንም አዲስ እውቀትና ሃሳብ መቀበል አቁመሃል። ‘’ በማለት ተናግሮ ብርጭቆውን ባዶ አድርጎ እንዲመለስ መከረው።  .

እኛም በህይወታችን ውስጥ በየቀኑ ተመሳሳይ ታሪክ ይከሰታል። ሁሉንም የምናውቅ ይመስለናል እናም ‘በትህትና ማዳመጥ እንዲሁም ከሌሎች መማር አያስፈልገንም!’ ብለን አእምሮአችንን ሞልተን ባዶ ማድረግ አቅቶናል!!!

🟢In Zen we don't Find the Answer , We loose the question" የምትል ግሩም አባባል አላቸው። ራስህን ባዶ አርገህ መማር ከፈለክ ዙሪያህ ሁሉ አስተማሪ ነው!  ሩቅ ሳትሄድ ከጎንህ ላለው ሰው ልብህን ክፈት፣ በመጠየቅ በመመለስ ሳይሆን በመረዳት እና በማስተዋል ነው አብርሆት የሚፈጠረው።

🟡የሰው ልጅ የነብሱን መንፈሳዊ ጎዳና ትክክለኝነት ማወቅ የሚችለው መንገደኛው ራሱ ነው..ስለ ሕይወትህ ችግር ከገጠመህ ወይም ጥያቄ ከተፈጠረብህ ዙርያህን አጥና... ያለህበት ሁኔታ ከሕይወትህ ጋር ያለውን አንድምታ መርምር በተለይ ትንሽ ትልቅ ሳትል በአቅራብያህ ያሉ ሰዎችን ህይወት በመመልከት ላንተ ምን መልእክት እንዳለው በትጋት ተከታተል ምክንያቱም የተፈጥሮ መንፈሳዊ አንደበት ናቸውና..."

🔴የተፈጥሮን መንፈሳዊ ቋንቋ ተማር ስትወድቅ ሆነ ስትነሳ ፍቺው ምን እንደሆነ ውስጥህን ጠይቅ  እውቀትን ሩቅ ፍልስፍና ወይም አንቃቂ ዲስኩሮች ውስጥ አትፈልግ፣ ከራስህ ጀምር ምክንያቱም የኩራዝ ብርሃንን ብታይ በደንብ የሚያበራው አቅራብያው ላለው ነው። አንተም ለራስህ ብርሀን ሁን መማር አታቁም፣ እድገትህን አትግታ፣ እራስህን አሻሽል፤  በአዳዲስ እውቀቶች እራስህን አንፅ!

ሁሌም ብርጭቆህን ባዶ አድርገህ ተነስ!

        ውብ ቅዳሜ ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🌗በአንድ ወቅት ጫካ ውስጥ መውለጃዋ የቀረበ አንዲት ሚዳቆ የመውለጃ ሰዐቷ ደርሶ ትግል ላይ ሳለች ድንገት አከባቢዋን ስትቃኝ ከፊት ለፊቷ ወንዝ ፣ ከኋላዋ ቀስት ያነጣጠረባትን አዳኝ፣ ወደ ጎን ስትዞር የተራበ አንበሳ አሰፍስፎባት ትመለከታለች።

ይህም ሳይበቃት ጭማሪ ከፍተኛ ነጎድጓድና መብረቅ ያጀበው ደመና መጥቶ ሰማዩን ያጨልመዋል። መብረቁም ሀይለኛ ስለነበር ደኑን ይመታውና ከፍተኛ ቃጠሎን ያስነሳባታል። ምን ታድርግ?

ወደ ፊት ሮጣ እንዳታመልጥ ጥልቅ ወንዝ ተደቀነባት፤ከኋላዋ አዳኙ፤ከጎኗ ደግሞ አንበሳው፤ወደ ጫካ ገብታ እንኳ እንዳትደበቅ ደኑ ከፍተኛ ቃጠሎ ላይ ነው...
በዚያ ላይ የውልደት ህመም ነፍስ ውጪ ግቢ እያስባላት ነው ...

💡ሚዳቆዋ በዚህ ውጥረት ውስጥ ሆና ትኩረቷን መፈፀም ወደ ምትችለው ነገር ላይ ብቻ በማድረግ ቀሪውን ለፈጣሪ በመተው በመወለድ ላይ ስላለው ልጇ ብቻ ማሰብ ጀመረች.....

አዳኙ ቀስቱን አነጣጥሮ ሊለቅ ባለበት ቅፅበት ድንገት የመብረቁ ብልጭታ አይኑ ላይ ብዥታ ፈጠረበትና ቀስቱ ተስፈንጥሮ ወደ ተራበው አንበሳ ይሄድና አንበሳውን ይገለዋል።

አጉበድብዶ የነበረው ደመናውም መዝነብ ይጀምርና የደኑን ቃጠሎ በቅፅበት አጠፋው። በጭንቅ ታጅባ የነበረችው ሚዳቆም በሰላም ተገላገለችና ወደ ቀደመው ህይወቷ ተመለሰች።

🔑አንዳንዴ በህይወትህ ውስጥ በብዙ ፈተናዎችና ጭንቀቶች ልትከበብ ትችላለህ፣ ያኔ አንተ ልትፈታው በምትችለው ነገር ላይ ብቻ አትኩርና ቀሪውን ለመፍትሄዎች ሁሉ ባለቤት ለሆነው ለፈጣሪህ ተወው።

መውጫ መፍትሄ አንተጋ እንጂ ፈጣሪህ ዘንድ አይጠፋም። አስታውስ ሁሌም ትላልቅ ወይም ከባባድ ፈተናዎች አሉብኝ ብለህ ለፈተናዎች እውቅና ከመስጠትህ ይልቅ የከባባድ ፈተናዎች አለቃ የሆነው ፈጣሪ አለኝ እያልክ ጭንቀቶችህን አቅልላቸው፣ሁሌም በፈጣሪህ ፈፅሞ ተስፋ አትቁረጥ!!!

📍ገጣሚ በረከት በላይነህ ''ሳይፀልዩ ማደር'' በምትለው ውብ ግጥሙ እንለያይ፣

''ሳይፀልዩ ማደር''

የተራበ ነብር ከሩቅ ተመልክታ
ሚዳቋ ፀለየች....
"አውጣኝ አውጣኝ" አለች ለፈጠራት ጌታ
...
ነብሩም ተርቦ
ወደ አምላኩ ቀርቦ
ሚዳቆዋን አይቶ - አንጀቱ ከሆዱ እንደተጣበቀ
ፈቅዶ እንዲሰጠው - አምላኩን ጠየቀ
...
የሁላችን ሰሪ
ፀሎታቸውንም ሰማቸው ፈጣሪ
አምላክም በድምፁ ሚዳቆዋን አላት
"እሩጠሽ አምልጪ ከበረታው ጠላት"
...
ነብሩንም አለው - "እሩጥ ተከተላት ምግብ አድርገህ ብላት"
ሚዳቆዋ ስትሮጥ
ከነብር ለማምለጥ
ነብሩም ሲከተላት
ሆዱን ሊሞላባት
.
ቋጥኙን ስትዘል እግሯ ተስፈንጥሮ
ሆዱን ብትረግጠው የተኛው ከርከሮ
ከእንቅልፉ ሲነቃ ልክ ሲደነብር
ጉሮሮውን ያዘው የፀለየው ነብር
...
አውጣኝ ያለው ወቶ አብላኝ ያለው በላ
ሳይፀልይ ያደረው ከርከሮ ተበላ

           ውብ አሁን ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity


💫እንኳን ለ 1445ኛው የዒድ አል ፈጥር በአል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
                
❤️በመላው አለም የምትኖሩ የእስልምና እምነት ተከታይ ሙስሊም ወገኖቻችን እንኳን ለ1443ኛው የዒድ  በአል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን።

✨ የዒድ በአል የእዝነት ÷ የመተሳሰብ ÷ አብሮ የመብላትና የመፈቃቀር በአል በመሆኑ በየ አካባቢያችን በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን እያሰብን እንዋል።

          ዒድ ሙባረክ !!!❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🔆ከራሱ ጋር የተስማማ ከተፈጥሮው ሁሉ ጋር ይስማማል!
(Live in harmony with nature)

📍ተፈጥሮ የሰው አካል ነው፤ ሰውም የተፈጥሮ ውህድ ነው፡፡ ሰው ከተፈጥሮ ውጭ መሆን አይችልም፡፡ ከተፈጥሮው ውጪ ልሁን የሚል ሰው ካለ መጀመሪያ የሚጋጨው ከራሱ ጋር ነው፡፡ ሁለተኛም ከልዕለ የተፈጥሮ ሃይል ጋር ይላተማል፡፡ ብዙ ሰው ከሰው ጋር ተስማምቶ መኖርን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ከራሱና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖርን አይደፍርም፡፡ ተፈጥሮው በማይፈቅደው መንገድ የሚተራመሰው ይበዛል፡፡ ያልሆነውን ለመሆን የሚፍጨረጨር የትየለሌ ነው፡፡ ሰው ከተፈጥሮው ከራቀና ከሰውነቱ ካፈነገጠ አደጋ ላይ ነው፡፡ አንድም አዕምሮው ማሰብ አቁማል፤ ሁለትም ጤንነቱ አጠራጣሪ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡

📍ጥንታዊው ሮማዊው ፈላስፋ ሴኔካ ለሚወደው ጓደኛው ለሉሲሊየስ በፃፈው ደብዳቤ ላይ፡- ‹‹ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተህ ከኖርክ በጭራሽ ደሃ አትሆንም፡፡ ነገር ግን እንደሌሎች ሃሳብ መኖር ከፈቀድክ ግን መቼም ቢሆን ሀብታም አትሆንም›› ብሎት ነበር፡፡ ሴኔካ ሀብትን ከቁስ ጋር አያይዞ አይደለም ይሄን የተናገረው፡፡ እሱ ሃብት የሚለው የመንፈስ ሀብትን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከተፈጥሮ ጋር በመግባባት የሚገኝ ነው፡፡ ተፈጥሮን ማወቅ፣ መረዳትና ከተፈጥሮው ጋር ተጣጥሞና ተስማምቶ መኖር ሰውን በመንፈሳዊ ሃብት እንዲበለፅግ ያደርገዋል፡፡ ብዙዎቻችን በመንፈሳችን ያጣን የነጣን ደሃ የሆንነው አንድም ተፈጥሮውን ለመረዳት ባለመጣራችን ነው፤ ሁለትም ሰውነታችንን ከተፈጥሮው ጋር እያቃረንን ስለምንኖር ነው፡፡

💡ብዙ ሰው በራሱ ሃሳብ ሳይሆን በሌሎች ሃሳብ ነው ኑሮውን የሚገፋው፡፡ ሰው ስለእሱ በሚሰጠው ፍረጃና አስተያየት እየተመራ ህይወቱን ሲኦል የሚያደርግ እልፍ ነው፡፡ በርግጥ የሁሉም ሰው አስተያየት ሰውን ገደል ይከታል ማለት አይደለም፡፡ የዛኑ ያህል የተሰጠን አስተያየት ሁሉ የመጨረሻው እውነትም አይደለም፡፡ በሁለቱ መካከል ማሰብና መመርመር የሚባል ነገር አለ፡፡ የትኛውንም መጤ ሃሳብ በአዕምሮ ወንፊትነት ማጣራት ግድ ይላል፡፡ ሳያኝኩ እንደሚውጡ ሳያስቡ የሰውን ሃሳብና አስተያየት የሚተገብሩ ራሳቸውን አደጋ ውስጥ ይከታሉ ለማለት ነው፡፡

💎ታዋቂውን የግሪኩን ፈላስፋ ዲዮጋንን አንዱ እንዲህ ብሎ ጠየቀው፡- ‹‹በሕይወትና በሞት መሐል ልዩነቱ ምንድነው?›› ዲዮጋንም፡- ‹‹ምንም ልዩነት የለውም›› አለው፡፡ ‹‹ታዲያ አንተ ለምን በሕይወት ትኖራለህ? ራስህን አታጠፋም ነበር?›› ሲለው፤ ዲዮጋንም፡- ‹‹እሱም ቢሆን ምንም ልዩነት የለውም!›› አለው ይባላል፡፡ ዲዮጋን ሞትንም ሕይወትንም አንድ ያደረገው ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ስለሆኑ ነው፡፡ ሞት ያለሕይወት፤ ህይወትም ያለሞት አልተፈጠረምና፡፡ ህይወትን ተቀብለህ ሞትን መተው አትችልም፡፡ ብዙዎች ከማያመልጡት ወጥመድ መሸሽ ይፈልጋሉ፡፡ ሞት የህይወትህ አካል ነው፡፡ የትም ብትሄድ አታመልጠውም፡፡ ይልቁንስ ህይወትንም ሞትንም ጠልቀህ ከተገነዘብክ አኗኗርህንና አኳኋንህን፤ መካከሉን ሕይወትህን እንድታስተካክል ይረዳሃል፡፡

📍የብዙዎቻችን አወዳደቅ ራሳችንን አለመሆናችን ነው፡፡ የእኛ የህይወት መስመር ከሌላው ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን ከራሳችን ተፈጥሮ ጋር ተራርቀን ስላለን ደረጃችንን የምንወስነው በሌሎች መለኪያ ነው፡፡ ዋናውና ስሜትን የሚጎዳው አወዳደቅ ደግሞ በትናንት ውድቀታችን ዛሬአችንን ስናወሳስበው ነው፡፡ ሁለቱም አወዳደቆች ከተፈጥሯችን ጋር በመጋጨት የሚመጡ ናቸው፡፡

💎ወዳጄ ሆይ... ከተፈጥሮው ጋር ተስማምተህ ኑር፡፡ ከራስህ አትራቅ፡፡ የአንተነትህን ተመን ራስህ አውጣ፡፡ ደስታም ይሁን ሀዘን ያለው አዕምሮህ ውስጥ ነውና በሌሎች መለኪያ ሕይወትህን አታወዳድር፡፡ ደረጃህን በራስህ ወስን፡፡ ሌሎች ምንም ብትሆን አቃቂር ከማውጣት አይቦዝኑም፡፡ ሌሎች እንዲያመሰግኑህ ብለህ ራስህን አትጣል፡፡

📍ለህሊናህ ታመን፡፡ ውስጥህን አድምጥ! ተፈጥሮህን እወቀው፤ እውነትን ተከተል፡፡ አንተነትህን አናግረው፡፡ መንፈስህን አበልጽገው፡፡ ዕለት ዕለት ከራስህ ጋር ትነጋገር ዘንድ ልመድ! ሞት የሕይወትህ ክፋይ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ መሄድህ ላይቀር ጥሩ ነገር ሰርተህ እለፍ! ከተፈጥሮውና ከተፈጥሮህ ተማር! ቀድመህ ከራስህ ጋር ተስማማ፤ ሌላው ቀሊል ነው!!

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🌗 ቅብጥብጡ ውሻ

✨የት እንዳነበብኳት ባላስታውስም ከረጅም ጊዜ በፊት ያነበብኳት አንዲት አጭር ታሪክ ትዝ አለችኝ፡፡ አስተምራኝ አልፋለች፣ ዛሬም ባሰብኳት ቁጥር ታስተምረኛለች፡፡ የአንድ ሰውና የውሻው አጭር ታሪክ ነው፡፡

💡በገጠራማው አካባቢ የሚኖር አንድ ሰው ከቤቱ ወጥቶ ወደ 30 ደቂቃ የሚፈጅ የእግር ጉዞ ካደረገ በኋላ መድረስ ወደሚገባው የወዳጁ ቤት ደረሰ፡፡ ከእሱ ጋር እሱ በሄደበት ሁሉ የሚከተለው በጣም የሚወደው ውሻው እንደተለመደው ተከትሎት መጥቷል፡፡ ሰውየው ወዳጁ ቤት ሲደርስ ከወዳጁ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ወዳጁ፣ “ያ ሁልጊዜ በሄድክበት ሁሉ የሚከተልህ ውሻህስ የት አለ?” ብሎ ገና ከመጠየቁ ውሻው እያለከለከና በውኃ ጥም ለሃጩን እያዝረከረከ ከባለቤቱ ጀርባ ከተፍ አለ፡፡

የዚህ ሰው ወዳጅ የሰውየውን አለመድከም ከውሻው ማለክለክ ጋር አነጻጸረና፣ “ውሻህን ምን አድርገኸው ነው እንደዚህ የደከመው፡፡ አንተ ምንም የድካ ስሜት አይታይብህም፣ እሱ ግን በጣም ደክሟል” አለው፣ ልክ በውሻው ላይ እንደጨከነበትና ችላ እንዳለው አይነት ስሜት በሚሰጥ ሁኔታ፡፡

💡የውሻውም ባለቤት ይህ የለመደውና በሄደበት ሁሉ ሰዎች የሚጠይቁት ጥያቄ በመሆኑ ብዙም ሳይገረም በውስጡ አቀባብሎ ያለውን መልስ መለሰለት፣ “የሚገርምህ ነገር ሁለታችን ከቤት ተነስተን እኩል መንገድ ነው የመጣነው፡፡ በእኔና በእሱ መካከል ያለው ልዩነት እኔ ቀጥ ብዬና ተረጋግቼ ነው የመጣሁት፣ እሱ ግን እንዴ ወደ ግራ፣ አንዴ ደግሞ ወደ ቀኝ ሲባዝን፤ አንዴ አንድን ነገር ሲያባርር፣ እንዴ ደግሞ ቆም ብሎ መሬቱን እያሸተተ አንድን ነገር አገኛለሁ ብሎ ሲቆፍ፣ እኔ ስርቅበት ደግሞ ለመድረስ ሲሮጥ . . . ሁል ጊዜ እሱን የሚያደክመው ይህ ቅብጥብጥ ባህሪው ነው”፡፡

💡ለካ ያለመጠን የሚያደክመን መንገዳችን ብቻውን አይደለም፣ ለካ የሚያዝለን ስራችን ብቻውን አይደለም፣ ለካ በቀኑ መጨረሻ ላይ ዝልፍልፍ የሚያደርገን የቀኑ ዋና ዓላማችን አይደለም፣ ለካ በኑሮ ድክም ያልነው በተለመደው የኑሮ ሂደት አይደለም፡፡ እኛን የሚያደክመንና ዝለት ውስጥ የሚከተን በመንገዳችን ላይ በማያገባን ነገር እየገባን ወዲህና ወዲያ የምንለው ነገር ነው፡፡

ይህ እውነት የገባኝ ቀን . . .

💎ስለማያገባኝ ሰው ማውራት አቆምኩኝ፣ በማያገባኝ ስፍራ መገኘት ተውኩኝ፣ ምንም ለውጥ በማያመጣ ነገር ላይ መከራከርን ጣልኩት፣ ምንም ተጽእኖ ከማላመጣለት ሰው ጋር መነታረክን ተወት አደረኩኝ፣ ድምዳሜ ላይ ስደርስ ምንም ፋይዳ የማያመጣልኝን ጉዳይ ማሰላሰል እርግፍ አደረኩኝ . . . በአጭሩ የማደርገው ነገር ሁሉ ከዋናው የህይወቴ ዓላማና እሴት ጋር የመጣጣሙን ጉዳይ ማሰብ መኖር ጀመርኩኝ፡፡

ይህንን ያደረኩኝ ጊዜ ብዙ ሸክም ከላዬ ላይ የተነሳ ያህል እርምጃዬ ቀለለኝ፣ ምክንያት-የለሹ የድካም ስሜት ተወኝ፣ የጀመርኩትን ግቤን ጥጉ የማድረስ ጉልበት አገኘሁኝ! ለካ እኔንም ልክ እንደ ቅብጥብጡ ውሻ ያደከመኝ ቀጥታው ሳይሆን ግራ-ቀኙ እና መለስ-ቀለሱ ነው!
   
✍ ዶ/ር እዮብ ማሞ

ውብ ጊዜ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

📍በሠዎች ዘንድ ተስፋ የሌለን ብንመስልም እንኳ ዋናው ነገር በፈጣሪ ዘንድ ያለው ተስፋችን ነው። ሕይወት ጠመዝማዛ ብትሆንም ውብና ተስፋን የተሞላች ናት።

💡በዚህ አለም ሁሉ ነገር አበቃ፣ አከተመ ባልንበት ጊዜ የሚቀጥል የተሻለ እድል፣ የምናውቀውና የተለመደው በር የተከረቸመ ቢመስልም ወለል ብሎ የሚከፈት ሌላ በር፣ ዙሪያችን ጭው ያለ በረሃ ቢሆንም የለመለመ መስክ የሆነ ስፍራ ላይ እንዳለ ተምሬያለሁ።

📍ህይወት እንደ ሳንቲም ናት ሁለት ገፅታዎች አሏት ፣ ተቃራኒ ግን ማይነጣጠሉ ገፅታዎች ። በህይወት እስካለን ካአንዱ ገፅ ብቻ ስንኖር ማለፍ የለም፣ እያንዳንዷ ሁኔታ ከጀርባዋ ተቃራኒ ገፅ አላት እናም ሳንቲም ያለ ግልባጭ ገፁ ምሉዕ እንደማይሆነዉ ያለ ሀዘን ደስታ ፣ ያለ ሞት ህይወት ፣ ያለ  ለቅሶ ሳቅ ፣ያለ ድህነት ሀብት ፣ ህይወትን ከነ ህብረ ቀለሟ አምነን መቀበል አለብን ፡፡

💡እድል ፊቷን ያዞረችብን በመሰለን ጊዜ እንኳ ቢሆን አብዝቶ በትጋት መጓዝ እንጂ ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ትጋት የተስፋ ልጅ ናት። ተስፋ ደግሞ በእኛና በፈጣሪ መካከል የእምነት ድልድይ ስለመኖሩ ማረጋገጫ ነውና!
"ዛፍ ቢቆረጥ ደግሞ ያቆጠቁጥ ዘንድ፣ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው" ።

✍አለማየሁ ዋሴ

ውብ አሁን♥️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍ @EthioHumanityBot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

🔺“ሰው - ራሱን እንኳ የሚያስደምመውን ተቃርኖ በውስጡ ተሸክሞ የማይፈራ።

“ሰው” -ጨክኖ መግደልን ከአፍቅሮ መግደል ጋር አስማምቶ ሲኖር እንቅልፍ የማያጣ።

ሰው' -ሰፍሮ ያልጨረሰው መሬት ቢጠበኝ ብሎ የሚሰፋ።

“ሰው -የስጋ ደካማነቱን ማካካሻ ከምናቡ ቆርጦ፥ በስራው፣ በሰራው እና በሚሰራው፤ ደካማነቱን የረታ፣ የሚረታ።

“ሰው -የማያቋርጥ የተቃርኖ ጅረት፣ የማይጠግ ጥበብ ምንጭ፤ የፍርሀት ልጅ፣ የድፍረት ወላጅ።

“ሰው - ምንነቱ ከማንነቱ የተምታታ፤ ምንነቱ ማለቂያ ቢስ፣ በማንነት የሚታሰር።

ሰው ፥ ይህ ሰው! እንዴትና በምን ?” ምንስ ሆኖ ?” ራሱን፣ ማንነቱን፣ ሰው-እነቱን ረሳ ?! ከዚህ በላይስ ምን ይገርማል !

📍ለማንኛውም ካላስታወሳችሁ አይፈረድባችሁም፡፡ ራሱን የረሳ ሰው፥ ሌላ ነገር አስታውስ ተብሎ ሊጠየቅ አይገባም፡፡ ግን ለምን አይገባም ?” ባይገባም፣ ባይገባም ግን ይጠየቃል፤ ይጠይቃል፣ ይመልሳል። የሆነውን ሳይሆን ያልሆነውን፣ የኖረውን ሳይሆን የተነገረውን፣ እውነቱን ሳይሆን የተባለውን ይመልሳል።

ሰው መሆን በጣም ይደንቃል። ሰው መሆኑን የረሳ ሰው፥ ወንድ መሆኑን ግን ሲያስታውስ አይደንቅም ?” ሰው መሆኑን የረሳ ሰው፥ ነጭ ወይም ጥቁር መሆኑን ሲያስታውስ አይደንቅም ?”

መሬት ላይ የተፈጠረ ሰው፥ መሬትን ረስቶ ሀገሩን ሲያስታውስ አይደንቅም ?” ከሌላው ጋር መግባቢያ ቋንቋ እንዳለውና ይህም ደግሞ ከየትኛውም ፍጡር እንደሚለየው ረስቶ፥ መናገሪያውን ማስታወሱ አይደንቅም ?”

ብትረሱም አልፈርድባችሁም። ዞሮ ዞሮ ምንም ነገር እንዳለኝ ወይም እንደነበረኝ ያወቅሁት፥ ሳይኖረኝ ሲቀር ነው። እናትም፣ ቋንቋም፣ ሀገርም፣ አያትም፣ አባትም፣ ሃይማኖትም ሁሉም፡፡

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍@EthioHumanitybot

Читать полностью…

ስብዕናችን #Humanity

✨«እናንተ የዓለም ብርሃን ፣ የምድርም ጨው ናችሁ»

🔷ብርሐንና ጨው ከተባልን ዘንዳ፤ እንግዲያውስ እውነተኛው ብርሐንና እውነተኛው ጨው ምንድነው አልን ! ቃሉን ልንተነትን ሳይሆን ቃሉ ያጫረብንን መረዳት ከአኗኗራችን ዘይቤ ጋር አዛምደን፣ በዘመናችን ታይታ ወዳድነት እና የመታየት ልክፍት፥ ሳናውቅ ለገባን እኛ ነገሩን ለማስታወስ ያህል ይህን አልን!

📍ብርሐን ያሳያል እንጅ አይታይም! ብርሐን የማይታየው ጨለማ ውስጥ ስለሆነ አይደለም፣ ይልቁንም ብርሐን ብርሐኑን የሚያበራው ወደራሱ ሳይሆን ወደሌሎች በመሆኑ ነው! ሌላውን ለማሳየት እንጅ ራሱን ለማጉላትና ለማድመቅ የሚታገል ብርሐን በዙሪያው የሚረጨው ጨለማ ብቻ ነው! እዚህ ላይ ብርሐን ስል የብርሃን ምንጩን ጭምር ማለቴ ነው።ብርሃን ተፈጥሮው ማሳየት እንጅ መታየት አይደለም።

🔷ፀሐይ በምትረጨው ብርሃን ዓለም ይነጋል ፤ ፍጥረት ሁሉ ይደምቃል፣ ተክሎች ያድጋሉ፣ አበቦችም ይፈካሉ፣ ቆፈን ይገፈፋል፤ ፀሐይን ራሷን ግን ለሴከንዶች እንኳን ማየት አንችልም።ታሳያለች እንጅ አትታይም! የቤታችንን አንፖል ከነመኖሩ የምናስታውሰው ቤታችን ሲጨልም ብቻ ነው፣ ግን ሁሉን ነገር የምናየው ከአንፖሉ በሚወጣው ብርሃን ነው። አንድ ሰው ሻማ የሚለኩሰው ሻማውን ሲያይ ለማምሸት አይደለም ፣ በሻማው ብርሃን አካባቢውን ሊያደምቅ ነው! መታየትን የምትሳሳ ነብስ ብርሐን አይደለችም፤ ይልቅ ብርሐን ያስፈልጋታል፤ በሌሎች ጨለማ የምትሳለቅ ነፍስ ብርሐን በውስጧ የለም ፣ብርሐን በተገኘበት የሌሎችን ጨለማ ያነጋል እንጅ በጨለማቸው አይዘባበትም።

📍ጨው እና ብርሃን ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፤ ጨው ብቻውን ምግብ ነኝ ብሎ ማዕድ ላይ አይኮፈስም፤ ቢኮፈስም የሚነካው የለም! ጨው ምግቡ ውስጥ አይታይም ግን ምግቡን ያጣፍጣል! በአጭሩ ነፍሳችሁ መታየትን መጉላትን መደነቅን መወደስን ከፈለገች «ሰዋዊ ነው» በሚል ትሁት መታበይ ራሳችሁን አታታሉ። እንደዛ ካሰባችሁ ብርሐንም ጨውም አይደላችሁም! እንደውም ትክክለኛ ጨውነታችሁ የሚታወቀው በእናተ በጎነት ሌሎች ሲወደሱ ነው! በተረት እንዝጋው «በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ» ይሄው ነው!

✍አሌክስ አብርሃም

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

✍@EthioHumanityBot

Читать полностью…
Subscribe to a channel