ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው። @tikvahuniversity @tikvahethAfaanOromoo @tikvahethmagazine @tikvahethsport @tikvahethiopiatigrigna #ኢትዮጵያ
#Houthis
የየመን ሁቲዎች በጉዞ ላይ የነበረ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ እና መርከቡ ቀይ ባህር ውስጥ ከሰጠመ በኋላ 6 መርከበኞች መትረፋቸውን እና ቢያንስ 3 ሌሎች ሰዎች መሞታቸውን የአውሮፓ የባህር ኃይል ተልዕኮ አስታወቀ።
የላይቤሪያን ባንዲራ የሚያውለበልበው እና በግሪክ የሚንቀሳቀሰው 'ኤተርኒቲ ሲ' የተባለው የጭነት መርከብ 25 ሠራተኞችን ይዞ እየተጓዘ ነበር።
መርከቡ ሰኞ ዕለት ከትንሽ ጀልባዎች በተተኮሱ የሮኬት ቦምቦች ከተመታ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በዚህም የመንቀሳቀስ አቅሙን እንዳጣ የእንግሊዝ የባሕር ንግድ ሥራዎች ኤጀንሲ (UKMTO) ገልጿል።
ጥቃቱ ማክሰኞ ዕለትም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን መርከበኞቹን የማዳን ሥራ የተጀመረው ሌሊት ላይ ነው።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች፤ ኤተርኒቲ ሲ ላይ ጥቃት የፈጸሙት ወደ እስራኤል እየተጓዘ ስለነበረ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ቁጥራቸው ያልታወቀ ሠራተኞችንም " ደህንነቱ ወደ የተጠበቀ ቦታ " እንደወሰዱ ተናግረዋል።
በየመን የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሁቲዎች " በሕይወት የተረፉ የቡድን አባላትን አፍነው መውሰዳቸውን " ገልጾ፤ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርቧል።
የፊሊፒንስ ባለስልጣናት ከቡድኑ አባላት ውስጥ 21 ያህሉ ዜጎቻቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።
ከቀሪዎቹ መካከል አንዱ የሩስያ ዜግነት ያለው እንደሆነ እና በጥቃቱ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት እግሩን እንዳጣም ተገልጿል።
ሁቲዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይህንን ዓይነቱን ጥቃት ሲፈጽሙ ይህ ሁለተኛቸው ነው።
ቡድኑ እሁድ ዕለት 'ማሲክ ሲስ' በተባለ ሌላ የላይቤሪያን ባንዲራ የሚያውለበልብ የግሪክ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
የእሁዱን ጥቃት የፈጸሙት መርከቡ፤ " በተወረረው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ በሚገኙ ወደቦች ላይ የተጣለውን የጉዞ ክልከላ የጣሰ ኩባንያ ንብረት በመሆኑ " ነው ብለዋል።
መረጃው የቢቢሲ ነው።
@tikvahethiopia
" ወደ 54 እንስሳት ነው የምናሳድነው፤ ኢንደሚክ የሆኑ ለምሳሌ ጭላዳ ዝንጀሮንም፣ የምኒልክ ድኩላንም እናሳድናለን " - የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን
በአራት ክልሎች ኢንደሚክ የሚባሉትን ጨምሮ ወደ 54 የኢትዮጵያ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን በውጪ ዜጎች እየታደኑ በዶላር እየተሸጡ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለስልጣን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገረ።
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት አጠቃቀም ባለሙያ አቶ ፋንታዬ ነጋሽ በሰጡን ገለጻ፣ ለምሳሌ " አንድ ኒያላ 15 ሺሕ ዶላር ነው የሚሸጠው፤ ይሄ ይበቃል? አይበቃም? የሚለው ገና እየታየ ነው በሕግ፤ አልጸደቀም እንጂ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ ገብቷል ረቂቁ። ዋጋው በቂ አይደለም " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ እንዲህ አይነት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መታደናቸው ልክ አይደለም የሚሉ ቁጣዎች እየተሰነዘሩ ነው፤ ለዚህ ትችት ያላችሁ ምላሽ ምንድን ነው ? ሲል አቶ ፋንታዬን ጠይቋል።
" ኢንደሚክ እንስሳት ይታደናሉ፤ ያም ደግሞ ዝም ብሎ በዘፈቀደ ሂዶ ማደን ሳይሆን ሳይንሳዊ በሚሆን መንገድ ተጠንቶ፤ ተቆጥረው ይህን ያክል ቢገደል ተብሎ በሚሰጥ ኮታ መሠረት ነው። የእንስሳቱን የመኖር ህልውና ምንም አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ተጠንቶ ነው ያ የሚደረገው፤ ያም ሲደረግ ደግሞ ከፌደራል፣ ከክልል የተውጣጡ ባለሙያዎች አጥንተው ሳይንሳዊ የሆነ ሪሰርች ቀርቦ ነው " ሲሉ አስረድተዋል።
" ወደ 54 እንስሳት ነው የምናሳድነው፤ ሁሉም የየራሳቸው ዋጋና ኮታ አላቸው። ኢንደሚክ የሆኑ ለምሳሌ ጭላዳ ዝንጀሮንም፣ የምኒልክ ድኩላንም እናሳድናለን " ብለዋል ባለሙያው።
ይህ የሚሆነው አንድ እንስሳ ምን ያህል ቢገደል ነው የእንስሳቱን ቁጥር የማይጎዳው? ተብሎ ቀንዱ ተለክቶ እድሜው ታውቆ እንደሆነ አስረድተው፣ "ለምሳሌ ኒያላን ከ29.5 ኢንቺ በታች ቱሪስቶች በስህተት እንኳ ከገደሉ የእንስሳውን እጥፍ ነው የሚከፍሉት። ማንኛውንም ሴት እንስሳ ቢገድሉ ደግሞ የዋጋውን እጥፍ እንዲከፍሉ ይደረጋል " በማለት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
በሌሎች ሀገራት የሌሉ ኢትዮጵያ ብቻ የምትታወቅባቸው ብርቅዬ እንስሳት እየታደኑ የሚሸጡ ከሆነ በአንድ ወቅት ህልውናቸው ሊጠፋ ስለሚችል ጭራሹንም መጠሪያ ማጣትን አያስከትልም ወይ? ከጠፉ ደግሞ የቱሪስት ፍሰት አይኖርምና ከሚገደሉ ይልቅ በቱሪስት የሚያስገኙት ገቢ አይሻልም ወይ? በሚል ለሚነሳው ስጋት ምላሽ እንዲሰጡም አቶ ፋንታዬን ጠይቀናቸዋል።
ምን መለሱ?
" ያልከው ስጋት ምናልባት ስፓርታዊ ሃንቲንግ ምንድን ነው? ብለው በትክክል ካለመረዳት የመጣ ነው። መስጋታቸው ምንም ሊደንቅ አይገባም፤ ግን ደግሞ ሳይንሱን ቢያውቁት ግልጽ ይሆንላቸዋል።
ሲቀጥል እንስሳቱ የሚታደኑት ፓርክ ላይ አይደለም። ይልቁንም ለእነርሱ ተብሎ የተከለለ የአደን ቀበሌ አለ፤ ከፓርኮቻችን ቢያንስ 5 ኪሎ ሜትር የራቀ ቦታ እንጂ ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ አደን አይፈቀድም። ነገር ግን ዓለም አቀፍ ህግ በሚፈቅደው መልኩ የአደን ቀበሌ ተብሎ ይቋቋልማል፤ እዚያ አደን ቀበሌ ላይ ነው ኮታ የሚሰጠው።
ኒያላ ብቻ ሳይሆን ወደ 54 እንስሳትን እናሳድናለን፤ አንድ ቱሪስት ደግሞ ኒያላ ብቻ ብሎ አይመጣም። ሌሎች እንስሳትን (የምኒልክ ድኩላ፣ ተራ ድኩላ፣ የቆላ አጋዘን...) አብሮ ይገዛል። ሁሉም በሳይንሳዊ መንገድ ተጠንተው ኮታ ተሰጥቷቸው ነው የሚታደኑት " ብለዋል።
በዚሁ አደንም ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝ፣ 85 በመቶው ገቢ እንስሳው ለታደነበት ክልል፣ 15 በመቶው ለፌደራል መንግስት እንደሚገባ፣ አደኑ በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች እንደሚከናወን፣ የታደኑትን እንስሳትን ትክክለኛ ቁጥር ለጊዜው ባያስታውሱም በዚህ ዓመት ወደ 177 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደተገኘ ገልዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#AddisAbaba
ሽንኩርት ፣ ድንችና ሌሎች የአትክልት ምርቶች #ከቫት ነጻ እንደሆኑ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አሳውቋል።
ቢሮው " ማህበረሰቡ ዕለት በዕለት የሚሸምታቸው ያልተዘጋጁ የአትክልት ምርቶች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ተደርገዋል " ሲል ገልጿል።
ከሰሞኑን ለቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች በወረደው ሰርኩላር ያልተዘጋጁ እንደ ሽንኩርት፣ ድንችና ሌሎች የአትክልት ምርቶች ከቫት ውጭ መደረጋቸውን አመላክቷል።
በሰርኩላሩ ላይ " የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 1341/2016 አንቀፅ 10 እና አዋጅን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 570/2017 ዓ.ም መሰረት ያልተዘጋጁ እንደ ሽንኩርት፣ ድንችና ሌሎች አትክልቶች ያሉ ምርቶች ወደሀገር ውስጥ ሲገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ ተመርተው ለግብይት ሲቀርቡ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ መደረጋቸውን ተደንግጓል " በሚል ተቀምጧል።
በዚህም መሰረት ያልተዘጋጁ የአትክልት ምርቶች የሚያቀርቡ ግብር ከፋዮች ብቻ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የተደረጉ መሆናቸው ታውቆ ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ተገቢው ክትትል በማድረግ እንዲፈፀም አዟል።
ይሁንና በአዋጁ ከታክስ ነፃ ከተደረጉ ውጪ የፍራፍሬ ምርቶች በሚያቀርቡ ግብር ከፋዮች የቫት አሰራሩ የሚቀጥል መሆኑን በመግለፅ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ ቢሮው አሳስቧል፡፡
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
@tikvahethiopia
" ካምፓኒዎቹን መቀመቅ የሚከት እብደት እንዲቆም የሚመለከተው አካል ሃላፊቱን ይወጣ " - አቶ በየነ ምክሩ
አሁን ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙትና የትእምት (EFFORT) ዋና ስራ አስፈፃሚ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ በየነ መክሩ ' ላዛ ትግርኛ ' ለተባለ የዩቱብ ሚድያ ቃለ መጠይቅ ሰጥተው ነበር።
በዚህም " ህገ-ወጥ " ሲሉ የጠሩት የደብረፅን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ህወሓት በትእምት ካምፓኒዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ እንዲያንዣብብ እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት ከሰዋል።
መጋቢት 2017 ዓ.ም በትግራይ በወቅቱ በነበረው ጊዚያዊ አስተዳደር ላይ በተከሰተው ከፍተኛ የፓለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መውጣታቸው የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው የሳቸውንና የባለ አደራ ቦርድ ሰብሳቢ ቴድሮስ ሓጎስ የሚጠቀሙበት ማህተም ከህግ አገባብ ውጪ በማስቀረፅ " ህገ-ወጡ ቡድን " አደገኛ ተግባራት በመፈፀም ላይ ይገኛል ብለዋል።
" ዋና ስራ አስፈፃሚ ፣ ቦርድና የባለ አደራ ቦርድ በስራ እያለ ቡድኑ የራሱ ህገ-ወጥ ቦርድና የባለ አደራ ቦርድ በመሰየም ዋና ስራ አስፈፃሚ ለመቅጠር ማስታወቅያ በማስነገር ላይ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ በየነ " ካምፓኒዎቹን መቀመቅ የሚከት ይህንን መሰል እብደት እንዲቆም የሚመለከተው አካል ሃላፊቱን ይወጣ " ብለዋል።
" የቡድኑ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ካምፓኒዎቹ ከስራ ውጭ እንዳያደርግ ከጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዜዳንት ታደሰ ወረደ (ሌ/ጀነራል) ተከታታይ ምክክሮች እያካሄድን ነው " ያሉ ሲሆን " ጉዳዩ በህግ-ማእቀፍ እንዲታይ በክልሉ ፍትህ ቢሮ ክስ መመስርተናል " ሲሉ አስታውቀዋል።
ይህን ሳይሳካ ከቀረ ግን የፌደራል መንግስት በትእምት ካምፓኒዎች ላይ በጦርነቱ ጊዜ ያስቀመጠው እግድ መልሶ ለማየት የሚገደድበት ሁኔታ ዝግ አይደለም ብለዋል።
በተጨማሪ ምን አሉ ?
- " የትእምት 60 በመቶ ሃብት በጦርነቱ ወድሟል ፤ መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ አርጅቷል ፤ ትራንስ ኢትዮጵያ ከነበሩት 500 መኪኖች አሮጌ 100 መኪኖች ብቻ ነው የቀሩት ፤ አልመዳ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በአውሮፕላን ቦንብ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። "
- " የፌደራል መንግስት ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም በትእምት ካምፓኒዎች ላይ አኖሮት የነበረው እግድ ለጊዜው ሲያነሳ ካምፓኒዎቹ ከህወሓት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው መስራት እንዳለባቸው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስጥቶ ነው ያስረከበን። "
- " የፌደራል መንግስት በትእምት ካምፓኒዎች ያስቀመጠው እግድ ሙሉ በሙሉ ባለነሳበት ሁኔታ ሆነን ከፓለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው እንዲያንሰራሩ ስንሰራ ነበር፤ ህገወጡ የህወሓት ቡድን ከካምፓኒዎቹ ላይ እጁ የማያነሳ ከሆነ የፌደራል መንግስት እግድ ሊቀጥል ይችላል። "
- " ህገ-ወጥ ቡድኑ በሃይል ካስቀመጣቸው አመራሮች የተደረገ ርክክብ የለም ፤ ዋና ስራ አስፈፃሚና ቦርድ የነበረው ነው ያለው። "
ትእምት ኢንቨስትመንት በስሩ 15 ካምፓኒዎች እንዳሉት ይታወቃል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
#TikvahEthiopiaFamilyMekelle
@tikvahethiopia
" በወረዳዎቹ በቂ የጸጥታ ኃይል የለም። ጥቂት የጸጥታ ኃይሎችም ታጣቅዎቹ ጥቃት ካደረሱና ዝርፊያ ከፈጸሙ በኋላ ይመጡና ወዲያው ይመለሳሉ " - ፓርቲው
ቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፣ " የ'ሸኔ' ታጣቂዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይ በመተከልና ካማሺ ዞኖች እያደረሱት ያለው ጥቃት ቀጥሏል " ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።
ፓርቲው ሰሞኑንም በወንበራ ወረዳ ጥቃት መድረሱን ገልጾ፣ " የክልሉ መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት በመስጠት በቂ የጸጥታ ኃይል በመላክና በአከባቢው የመከላከያ ካምፕ በማቋቋም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት እንዲያስጠብቅ " ጠይቋል።
" በካማሺ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች፣ በመተከል ዞን በቡለን፣ ድባጢና ወምበራ ወረዳዎች ታጣቂዎቹ የሚያደርሱት ጥቃት ተጠናክሮ ቀጥሏል " ያለው ፓርቲው፣ " ታጣቅዎቹ ንጹሐንን እና የጸጥታ አካላትን ይገድላሉ፣ የግልና የመንግስት ሀብት፣ ንብረት፤ የመንግስት ተቋማትን ይዘርፋሉ፤ ያወድማሉ " ሲልም ከሷል።
" ባለፈው ወር ቡለን ከተማ፣ ድባጢ ወረዳ በርበር ከተማ ሁለት ጊዜ ጥቃት ያደረሱ ሲሆን፣ በቡለን ከተማ በአንድ ሌሊት ብቻ የአረፋ በዓል በማክበር ላይ የነበሩ 11 የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትን ከመግደል ባለፈ በርካታ ንጽሐንን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና የጸጥታ አካላት ገድለዋል፤ ንጽሐንን አግተዋል " ብሏል።
ታጣቂዎቹን ተቋማትን " ዘርፈዋል፤ አውድመዋል " ሲል የከሰሰው ፓርቲው፣ " ሰሞኑን በወምበራ ወረዳ ወግዲና ሌሎች ቀበሌዎች ተመሳሳይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል። ይህ ታጣቂ ቡድን በድባጢ ወረዳ ከ60% በላይ፣ በቡለን ወረዳ ከ30% በላይ ቀበሌዎችን በራሱ ቁጥጥር ስር በማደርግ ሰሞኑን ደግሞ በወንበራ ወረዳ በወግዲ ቀበሌ ግዛቱን ለማስፋፋት እየጣረ ይገኛል " ሲል ጠቁሟል።
ፓርቲው፣ " የሸኔ ታጣቂዎች በየወረዳዎቹ በሚኖሩ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ላይ ነው ጥቃት የሚያደርሱት " ብሎ፣ " በዚህ ምክንያት ነዋሪዎቹ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። በርካቶችም ተፈናቅለው ወደ አጎራባች ከተሞችና ወረዳዎች እየሄዱ ይገኛሉ " ብሏል።
" ታጣቂዎቹ በወረዳዎቹ ይህንን ሁሉ ጥቃት ሲፈጽሙና ወረዳዎች ‘ካቅማችን በላይ ነው’ እያሉ ለክልሉ መንግስት ሲያሳውቁ የክልሉ መንግስት ግን ለምን በቂ ትኩረት መስጠት እንዳልፈለገና ህዝቡን መከላከል ለምን እንዳልቻለ ለእኛ እንቆቅልሽ ሆኗል " ነው ያለው።
ፓርቲው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ " ህዝቡም በተደጋጋሚ ለክልሉ መንግስት የይድረሱልኝ ጥሪ ቢያቀርብም ሰሚ አላገኘም። በወረዳዎች በቂ የጸጥታ ኃይል የለም። ጥቂት የጸጥታ ኃይሎችም ታጣቅዎቹ ጥቃት ካደረሱና ዝርፊያ ከፈጸሙ በኋላ ይመጡና ወዲያውኑ ወይንም በነጋታው ይመለሳሉ " ሲል ነው የገለጸው።
" ህዝቡ ከፍተኛ ስጋት ላይ ይገኛል። ከሁሉም በላይ ይህ ሁሉ ጥቃትና በደል በህዝቡ ሲደርስ ክስተቱ በየትኛውም የመንግስት ሚዲያ አለመዘገቡና ሽፋን አለማግኘቱ ህዝቡን አሳዝኗል " በማለትም ወቅሷል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#SafaricomEthiopia
⚡️ በዕለታዊ የዳታ ጥቅሎች ዘና ፈታ እንበል! 🥳
በልዩ ልዩ አማራጮች የቀረበልንን የሳፋሪኮም የኢንተርኔት ጥቅል የM-PESA Appን በመጠቀም አሁኑኑ እንግዛ! በፈጣን ዳታ እንንበሽበሽ!
#1wedefit
#Furtheraheadtogether
#Axum
የአክሱም ከተማ ፖሊስ በከተማው ክንደያ በተባለ ቀበሌ ሁለት ተጠርጣሪዎች አደገኛ ኬሚካል በመጠቀም የወርቅ ማጣራት ተግባር ሲያከናውኑ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው አሳውቋል።
ፖሊስ ከህብረተሰብ በደረሰው ጥቆማ የፍ/ቤት የፍተሻ ትእዛዝ በመያዝ የተለያዩ የፍትህ አካላት ፣ የአገር ሽማግሌዎችና የጤና ባለሙያዎች በማሳተፍ ነው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ያዋላቸው፡፡
የከተማዋ አቃቤ ህግ የህበረተሰብ የጤና ጠንቅ የሆነውን አደገኛ ኬሚካል በመጠቀም ህገወጥ ተግባር ሲፈፅሙ የተገኙት ተጠርጣሪዎቹ በአጭር ጊዜ አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ከባለ ድርሻ አካላት በመሆን ይሰራል ብሏል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
Photo credit - Tigrai Television
@tikvahethiopia
#AddisAbaba
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2017 ዓ/ም የግብር ዘመን ግብር አወሳሰንና አሰባሰብ አሰራር ይፋ አድርጓል።
አዲሱ መመሪያ የሂሳብ መዝገብና የሂሳብ መግለጫ መሰረት በማድረግ የማሳወቅ፣ የመክፈል እና ሰነዶችን የመያዝ ግዴታ ተፈጻሚ የማይደረግባቸው ግብር ከፋዮችን በሚመለከት።
እንዲሁም የሂሳብ መዝገብና የሂሳብ መግለጫ መሰረት በማድረግ የማሳወቅ፣ የመከፈል እና ሰነዶችን የመያዝ ግዴታን ያልተወጡ ግብር ከፋዮችን በተመለከተ መደረግ ስላለበት ዝርዝር ሃሳብ የያዘ ደብዳቤ በቢሮው የታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ወርቅነሽ ሰቦቃ ተፈርሞ ለሁሉም ለግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተልኳል።
ደብዳቤው "የተወሰኑ ግብር ከፋዬች በህጉ የተጣለባቸውን ግዴታ ለመወጣት የተሰማሩበትን የስራ ዘርፍ ባለው የተለየ ባህሪ ምክንያት መቸገራቸውን በተለያየ ጊዜ በመጥቀስ አቤቱታ ያቀረቡ" መሆኑን ገልጿል።
ይሁን እንጂ የግብር ሕጉ ለየትኛውም የንግድ ዘርፍ በተለየ መልኩ የሂሳብ መዝገብና የሂሳብ መግለጫ መሰረት በማድረግ የማሳወቅ የመከፈል እና ሰነዶችን የመያዝ ግዴታን ቀሪ አለማድረጉንም አሳውቋል።
ይህንኑ ግዴታ አለመወጣትም አስተዳደራዊ ቅጣት የሚያስከትል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተለየ ባህሪ ያላቸው የተወሰኑ የሥራ ዘርፎች የግብር ህጉን ድንጋጌዎች በአስከበረ አግባብ የገቢ አሰበሰቡን እና የአገልግሎት አሰጣቱን ፍታሀዊነት ማዕከል ያደረገ የአሰራር ሥርዓት ለ2017 የግብር ማሳወቂያ ጊዜ ሂሳብ መዝገብ የማቅረብ ግዴታን ተፈጻሚነት በቅጣት ብቻ በማለፍ ማዘግየት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ብሏል።
ስለሆነም የደረጃ "ሀ" እና የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዬች የሂሳብ መዝገብና የሂሳብ መግለጫ መሰረት በማድረግ የማሳወቅ፣ የመከፈል እና ሰነዶችን የመያዝ ግዴታን ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ግብር ከፋዬች በማይወጡበት ጊዜ ለደረጃ «ሐ» ግብር ከፋዬች የወጣውን ገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 የትርፍ ሕዳግ እና በግምት ግብር አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 138/2010 በቁርጥ የወጪ ሰንጠረዥ መጠቀም ዘርፉ ግዴታውን በገቢ ግብር ሕጉ መሰረት እንዳይወጣ ከተማውም ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳይሰበስብ ምክንያት ስለሚሆን ይህንኑ ክፍተት ለመዝጋት በገቢ ግብር አዋጁ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 80 መሰረት ግብር በግምት በሚሰላበት ጊዜ፦
ከግብር ከፋዮች ግንዛቤ የተለየ ድጋፍ የሚፈልጉ እና ሥራቸውም ከመንግስት ጋር በተገባ ውል ብቻ የሚያከናውኑ በማህበር የተደራጁ :-
- የትምህርት ቤቶችና የምገባ ማዕከላት መጋቢ እናቶች
- በከተማ ጽዳትና ውበት ደረቅ ቆሻሻ እና ገጸ-ምድር ማስዋብ ላይ የተሰማሩ
- ከንግድ ቢሮ ትስስር የተፈጠረላቸው የሸገር ዳቦን የሚሸጡ ማህበራት
ከመንግስት ተቋማት ጋር ያላቸውን ውልና በበጀት ዓመቱ ከአሰራቸው የመንግስት ተቋም ዓመቱን ሙሉ የተከፈላቸውን ክፍያ የሚገልጽ መረጃ ሲያመጡ መረጃን መሰረት አድርጎ በሠንጠረዥ "ሐ" መሠረት ግብሩን በማስላት ገቢው ተወስኖ እንዲሰበሰብ።
በተጨማሪም የሸገር ዳቦን የሚሸጡ በተጓዳኝ የሚከናውኑ የንግድ ስራዎች መኖራቸው በመስክ ምልከታ ተረጋግጦ በየዘርፉ የቀን ገቢ ግምት እንዲገመትላቸው ተደርጎ ግብሩ ተወስኖ እንዲሰበሰብ።
የንግድ ሥራ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሞያ ፍቃድ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ጠበቆች ፣የኢንሹራንስ ወኪሎች ፣ኢንሹራንስ ጉዳት ገማች ግለሰቦች በሚመለከት:-
➡️ ከግብር አመቱ አጠቃላይ እንደ ገቢ 35 በመቶ እንደ ወጪ 65 በመቶ ግብር የሚከፈልበት ገቢ ሆኖ በሠንጠረዥ "ሐ" መሠረት ግብሩን በማስላት ተወስኖ ገቢው እንዲሰበሰብ።
➡️ የንግድ ሥራ ያልሆነ ገቢ ያላቸው የመኖሪያ ቤት አከራዮች ከግብር አመቱ አጠቃላይ ገቢ 35 በመቶ እንደ ወጪ 65 በመቶ ግብር የሚከፈልበት ገቢ ሆኖ በሠንጠረዥ "ሐ" መሠረት ግብሩን በማስላት ተወስኖ ገቢው እንዲሰበሰብ።
➡️ በግል ኮድ 02 እና በንግድ ኮድ 03 ተሸከርካሪ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ አጠቃላይ የኪራይ ገቢ ላይ በሠንጠረዥ "ሐ" መሠረት በመረጃ የሚወሰን በመሆኑ ግብሩን በማስላት ተወስኖ ገቢው እንዲሰበሰብ።
➡️ በህግ ደረሰኝ የመጠቀም ግዴታ ተፈጻሚ የማይደረግባቸው የከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች /በቴክኖሎጂ ስምሪት የሚሰጣቸውን የሜትር ታከሲዎች ጨምሮ/ የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 ሠንጠረዥ "ሐ" መሠረት ግብሩን በማስላት ተወስኖ ገቢው እንዲሰበሰብ መወሰኑን ይገልጻል።
(ተጨማሪውን ከተያያዘው ደብዳቤ ይመልከቱ)
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAddisAbaba
@tikvahethiopia
" ህልምን ለማሳካት ቆራጥ መሆን ያስፈልጋል " - ከሶስተኛ ልጃችው ጋር ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተቀመጡት የ52 አመቱ አባት
ዛሬ ከሶስተኛ ልጃቸው ጋር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየወሰዱ ያሉት የ52 አመቱ አባት አቶ ግዛው መኮነንን ነዋሪነታቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን በአዳኝ ሀገር ጫቆ ወረዳ ነው።
ከሚኖሩበት ነጋዴ ባህር ከተማ ህዝብ ተሰብስቦ " መልካም እድል " ብሎ መርቆ ወደ ጎንደር ዮንቨርስቲ ከልጃቸው ጋር ሸኝቷቸዋል።
አቶ ግዛው መኮነን የ5 ልጆች አባት ሲሆኑ የ52 አመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው።
" በ1979 ዓ.ም የ6ተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ ያውም ጎበዝ አንድ አንደኛ የምወጣ ተሸላሚ ተማሪ ነበርኩ ግን በወቅቱ አስገዳጅ በሆነ ምክንያት ትምህርቴን አቋረጥኩ " ይላሉ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
አቶ ግዛው " ትምህርቴን እንዳቋርጥ ያስገደዱኝ ወላጆቼ ናቸው በወቅቱ ደርግ በግዳጅ ለውትድርና ወጣቱን ይመለምል ነበር ያኔ ወላጆቼ ወደ በርሃ እንድገባ አስገደዱኝ ማለትም 1979 ዓ.ም ከአራት አመት የበርሃ ቆይታ በኃላ ወደ ትውልድ ከተማየ ስመለስ በ1983 ዓ.ም ማለት ነው ጏደኞቼ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሆነው አገኘኃቸው " ብለዋል።
" በዚህ ልዩነትማ ትምህርት አልጀምርም አንዴ ኃላ ቀርቻለሁ ብየ ሚስት አገባሁ ከዛም በተከታታይ 5 ልጆችን ወለድኩ ልጆቼን ለማሳደግም በግብርና ኃላም በንግድ ስራ ተሰማራሁ 5ተኛ ልጄን ከወለድኩ በኃላ የዛሬ 6 አመት ማለት ነው በማታው ትምህርት ክፍል ካቆምኩበት 6ተኛ ክፍል ቀጠልኩ በርትቼ በማጥናትም ለዛሬ ፈተና ደርሻለሁ " ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ ግዛው ያኔ አብረዋቸው የተማሩ ጏደኞቻቸው እስከ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የደረሱ እንዳሉና በሚኖሩበት አካባቢም ፖሊስና መምህር ሆነው ህዝብን ሲያገለግሉ ሲመለከቱ ይቆጩ እንደነበር ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት በግብርና ስራ ልጅን የማሳደግ ኃላፊነት ይዘው ህይወታቸውን ቢገፉም ጎን ለጎን የትምህርያቸው ጉዳይ ያንገበግባቸው ነበር።
የአቶ ግዛው የመጀመሪያ ልጃቸው በንግድ የተሰማራ ሲሆን ሁለተኛ ልጃቸው የግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ ናት ሶስተኛ ልጃቸው ዛሬ ከእርሳቸው ጋር በጎንደር ዩንቨርስቲ ሀገር አቀፍ ፈተናውን እየወሰደ ነው ፤ አራተኛና አምስተኛ ልጆቻቸው ተማሪዎች ናቸው።
" ህልም ለማሳካት ቆራጥ መሆን ያስፈልጋል " የሚሉት አቶ ግዛው ፈተናውን ለመውሰድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና ከልጃቸው ጋር እስከ እኩለ ሌሊት አብረው ሲያጠኑና ሲረዳዱ መክረማቸውን ተናገረዋል።
ለዩንቨርስቲ መግቢያ የሚያበቃ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀታቸውን ውጤቱ ቢመጣም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት መዘጋጀታቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ባሕር ዳር
#TikvahEthiopiaFamilyBahirdar
@tikvahethiopia
#Update
" የዘገየ ፍትህ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል ! " - ሂደቱን የሚከታተሉ ታዛቢዎች
አሁንም የእንስት ዘወዱ ሃፍቱ የግድያ ወንጀል የፍርድ ውሳኔ ሌላ ቀጠሮ ተይዞለታል።
የግድያ ወንጀሉ ከተፈፀመ የፊታችን ነሀሴ ወር የሚከበረው የአሸንዳ 2017 ዓ.ም በዓል ሁለት ዓመት ይሞላዋል።
አሰቃቂ የግድያ ወንጀሉ የአሸንዳ በዓል በሚከበርበት ወርሃ ነሀሴ 2015 ዓ.ም ነበር የተፈፀመው።
የእንስት ዘውዱ ሃፍቱ የግድያ ወንጀል ችሎት የትላንት ውሎ ምን ይመስል ነበር ?
የእንስት ዘውዱ ሃፍቱ የግድያ ወንጀል በመመልከት ላይ የሚገኘው የመቐለ ማእከላዊ ፍርድ ቤት ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም በተከሳሾች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ላይ ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች የሚያቀርቡት የፍርድ የማቅለያ ለመስማት ነው ለሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የተቀጠረው።
የችሎቱ ዳኞች በያዙት ቀጠሮ ተከሳሾች ለፍርድ ማቅለያ የሚሆናቸውን የህክምናና ሌሎች ሰነድ እንዲያቀርቡ ባዘዙት መሰረት በጠበቃቸው በኩል አቅርበዋል።
አንደኛ ተከሳሽ የልብ ህመም ታማሚና የኪንታሮት ህመምተኛ ፣ ሁለተኛው ተከሳሽ ደግሞ የስኳርና የኪንታሮት ህመምተኛ መሆናቸውን በቃል ቢገልጹም በሃኪሞች ማስረጃ እንዲረጋገጥ ለሀምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በግድያ ወንጀሉ በመፈፀመ የተጠረጠሩ ሁለቱ ወጣቶች ሀምሌ 3 ቀን 2017 ዓ/ም በሃኪም የተረጋገጠ የፅሁፍ ማስረጃ ያቀርቡ እንደሆነ ያኔ የሚታይ ሆኖ የችሎት ሂደቱን የተከታታሉ የሚድያ ባለሙያዎች ፣ የሴቶች ጥቃት እንዲቆም የሚሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት " ይህንን ሁሉ በሽታ ተቋቁመው ይህን መሰል ዘግናኝ ግድያ ለመፈፀም እንዴት ጉልበትና አቅም አገኙ ? " የሚል ጥያቄ ጭረዋል።
የችሎቱ የውሎ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ የተከታተሉ በርካቶች የፍርድ ሂደቱ ለሁለት አመታት መራዘሙ በመቃወም " የዘገየ ፍትህ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል " ብለዋል።
የአሰቃቂ የግድያ ወንጀሉ የፍርድ ሂደት ሀምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም መቋጫ ይብጀለት ይሆን ? ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ጉዳዩ ተከታትሎ ያቀርባል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
#TikvahEthiopiaFamilyMekelle
@tikvahethiopia
#Wolaita
ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በም/ማዕረግ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነ ተሾሙ። ወ/ሮ እታገኝ ሀ/ማሪያምን ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ሆነዋል።
የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደዉ አስቸኳይ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን አፅድቋል።
በዚህም ፦
1. ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በም/ማዕረግ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ
2. አማረ አቦታ (ዶ/ር) የወላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ
3. አቶ ተስፋሁን ታዴዎስ የወላይታ ዞን ም/አስተዳዳሪና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ
4.ወ/ሮ እታገኝ ሀ/ማሪያምን የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ አድርጎ በሙሉ ድምጽ ሾሟቸዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
#TikvahEthiopiaFamilyHawassa
@tikvahethiopia
#HoPR🇪🇹
" ድንጋጌውን ' ትክክል ነው ' ብለው ሲከራከሩ የነበሩ የፓርላማ አባላት ነበሩ፤ ዛሬ ደግሞ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መደገፋቸው በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ያስብላል " - የፓርላማ አባል
በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን " በሽፋን ስር " ሆኖ የመመርመር ኃላፊነት የተሰጠው ሰው፤ " ከግድያ በስተቀር " የሚፈጽማቸውን የወንጀል ድርጊቶች ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርገው ድንጋጌ ተሰረዘ።
ድንጋጌው የተሰረዘው አዋጁ " በሰፊው እንዲተረጎም ስለሚያደርግ " እና በአተገባበሩም ላይ " አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያስከትል ስለሆነ ነው " ተብሏል።
አወዛጋቢው ድንጋጌ ተካትቶ የነበረው፤ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ላይ ነበር።
አዲሱ አዋጅ በፓርላማ የጸደቀው ሰኔ 10፤ 2017 ዓ.ም. ነበር።
የተሰረዘድ ድንጋጌ " በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ወይም በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍን እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰው፤ በግዴታው ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፈቃዱ ውጭ ሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም " ይላል።
አዋጁ በጸደቀበት ዕለት የውሳኔ ሃሳብ ለፓርላማ አባላት ያቀረበው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚቴ፤ ድንጋጌው እንዲካተት የተደረገው " ልዩ የምርመራ ስራን " " ውጤታማ የሚያደርግ በመሆኑ "ምክንያት እንደሆነ ገልጾ ነበር።
ቋሚ ኮሚቴው " ልዩ የምርመራ ዘዴን " በመጠቀም ስራውን የሚያከናውን ሰው፤ " የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰራ መሆኑን " እንደ ደጋፊ ምክንያት አቅርቦ ነበር።
ይሁንና ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ ሰኞ ሰኔ 30 በተደረገ የተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ፤ ድንጋጌው እንዲሰረዝ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።
ድንጋጌው " አዋጁ በሰፊው እንዲተረጎም የሚያደርግ እና አተገባበሩ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ የሚያስከትል ስለሆነ፤ አዋጁ ለህትመት ያልበቃ እና በሂደት ላይ ያለ በመሆኑ፤ ቀሪ እንዲሆን ይህ የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል " ብሏል።
የውሳኔ ሀሳቡ በአንድ ድምጽ ተዐቅቦ ፀድቋል።
የፓርላማ አባላት ምን አሉ ?
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የፓርላማ ተወካይ አቶ ባርጠማ ፈቃዱ ፦
" አዋጁ ተመልሶ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምጣቱ የምክር ቤቱን አቅም ጭምር የሚያሳይ ነው።
አዋጁ በሚጸድቅበት ወቅት ድንጋጌውን ' ትክክል ነው ' ብለው ሲከራከሩ የነበሩ የፓርላማ አባላት ነበሩ፤ ዛሬ ደግሞ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መደገፋቸው በአንድ ራስ ሁለት ያስብላል " ብለዋል።
ሌላ የፓርላማ አባል ፦
" አዋጁ በሚጸድቅበት ጊዜ በድንጋጌው ላይ በመሰረታዊነት ክርክር ተደርጓል። በድንጋጌው ላይ የተለያየ መልክ ያለው ጫጫታ በብዛት ሲሰማ ነበር።
በምርመራ ወቅት የሚመረምረው አካል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለበት ጊዜ፤ ከዚህ ውጪ ሊያደርግ የሚችለው ጉዳይ እንደሌለ፣ ዋስትና ሊያገኝ እንደሚገባ በደንብ ማብራሪያ የተሰጠበት ጉዳይ ነበር።
ድንጋጌው ከአዋጁ ውስጥ እንዲወጣ ሲደረግ፤ መርማሪዎች የተሰጣቸውን ዋስትና የሚያስቀር በመሆኑ ቀድሞ የጸደቀው ባለበት ቢቀጥል ይሻል ነበር።
የሚመረምሩ ሰዎች፣ አደገኛ ችግር ውስጥ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ፤ የእዚህ አይነት ዋስትና ሊያገኙ የማይችሉ ካልሆነ ሊመረምሩ ፍቃደኛ ይሆናሉ ወይ? ሊገቡ ፍቃደኛ ይሆናሉ ወይ? የሚመረምሩ ሰዎች አደገኛ ችግር ውስጥ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ዋስትና የማንሰጣቸው ከሆነ፤ እንደዚህ አይነት risk ሊወስድ የሚችል አካል ላይኖር ይችላል። " ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ምን አሉ ?
" ለእንደዚህ አይነት የምርመራ ስራዎች ዋስትና የሚሰጥ ህግ አለ። ዋስትና መስጠት እና ሌላ ነገር እንዲያደርግ ማድረግ የተለያየ ነገሮች ናቸው። ድንጋጌው መሰረዙ ተገቢ ነው። "
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ ነው።
@tikvahethiopia
#Tigray
" በትግራይ በኩል የሚከፈት ጦርነት የለም ፤ ከሌላው ወገን የሚተኮስ ጥይት እንዳይኖር ጥንቃቄ ያሻል " - የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት
" በትግራይ በኩል የሚከፈት ጦርነት የለም ፤ ከሌላው ወገን በተሳሳተ ውሳኔ ትግራይ የሚተኮስ ጥይት እንዳይኖር ጥንቃቄ ያሻል " ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ታደሰ ወረደ (ሌ/ጀነራል) ተናገሩ።
ፕሬዜዳንቱ " ሁሉም ነገር በሰላማዊ መንገድ ይፈታል ብለን ስለምናምን በትግራይ በኩል የሚጀመር ትንኮሳ እና ጦርነት አይኖርም " ብለዋል።
" በክልሉ ደቡባዊ ዞን ያለው ችግር የመላው ትግራይ እንጂ የአከባቢው ብቻ አይደለም " ያሉት ፕሬዜዳንት ታደሰ " ጊዚያዊ አስተዳደሩ በዞኑ ካለው አስተዳደር በመነጋገር በሰላማዊ መንገድ ይፈታዋል " ሲሉ ተናግረዋል ።
ራሱን " የትግራይ የሰላም ሃይል " በሎ ከሚጠራውና በዓፋር ክልል ሆኖ የትጥቅ ትግል ከሚያካሂደው ሃይል ጋር ያለውን ችግር " በሰላማዊ ውይይት ይፈታል " ያሉ ሲሆን " ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ ግን ህዝብን ለአደጋ የሚዳርግ ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል " ብለዋል።
" የትግራይ ሉአላዊነት ተደፍሮ ተፈናቃዮችና ስደተኞች ወደ ቄያቸው ባልተመለሱበት ሁኔታ ላይ ተሆኖም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ የመንፍታት ጉዳይ አንደኛ አማራጫችን ነው " ሲሉ ተደምጠዋል።
" ተፈናቃዮችና ስደተኞች ወደ ቄያቸው መመለስ ከሁሉም ስራዎቻችን ቅድምያ የምንሰጠው ነው ጉዳዩ ጊዜ በወሰደ ቁጥር የሰላም በር እንዳያጠብ የፌደራል መንግስት የበኩሉን ሃላፊነት በመወጣት ችግሩ እንዲፈታ ጥሪ እናቀርባለን " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
#TikvahEthiopiaFamilyMekelle
@tikvahethiopia
#Update
19 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል !
ታዳጊዋ አያንቱ ቱና ላይ የግበረስጋ ድፍረት የፈጸመው ግለሰብ በ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።
በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ሻፋሞ ወረዳ የ13 ዓመቷን ታዲጊ አያንቱ ቱና ላይ የግብረስጋ ድፍረት ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠረውና በፖሊስ ተባባሪነት ጭምር አምልጦ ከ1 ዓመት በላይ ተሰዉሮ የነበረዉ ወጣት በቲክቫህ ኢትዮጵያ ላይ መረጃው ከተሰራጨ በኋላ በተደረገ ክትትልና ፍለጋ ተጠርጣሪዉ በቁጥጥር ስር ዉሎ ክስ ተመስርቶበት እንደነበር የአያንቱ ታላቅ ወንድም ወጣት ጴጥሮስ ቱና ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።
ይኸው ግለሰብ አርብ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቦ ዉሳኔ እንደተላለፈበት የአያንቱ ወንድም ተናግሯል።
የሻፋሞ ወረዳ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደምሴ ፉና ስለጉዳዩ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ሲያስረዱ " የወረዳዉ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ ያቀረቡትን ጠንከር ያለ ምርመራ፣ የሰነድ እንዲሁም የሕክምና ማስረጃዎችን የተመለከተዉ የወረዳዉ ፍርድ ቤት ግለሰቡን ጥፋተኛ ነዉ በማለት በ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል " ብለዋል።
" ተጠርጣሪዉ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በማቆያ ዉስጥ የምትገኘዉ አያንቱ ደፋሪዋ እንደተያዘ ከተነገራት በኋላ ጥሩ መሻሻል ታይቶባታል " የሚለዉ የታዳጊዋ ወንድም ጴጥሮስ " ከዚህ በኋላ ከማቆያ ወጥታ ወደ ትምህርት ገበታዋ ትመለሳለች " ብሏል
" የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ለታዳጊዋ ድምፅ ለሆናችሁ ሁሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ " ብሏል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
#TikvahEthiopiaFamilyHawassa
@tikvahethiopia
" ከ47 በመቶ በላይ አሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ከፍጥነት ወሰን በላይ ነው የሚያሽከረክሩት ! "
የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማኀበር ዘርፉን በተመለከተ አዘጋጅቶት በነበረው መድረክ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጀመንት ባለስልጣን መጥተው የነበሩት አቶ ደረጀ የተባሉ አካል " በየዓመቱ ከ2000 እስከ 300ዐ ለሚሆኑ አሽከርካሪዎች ስልጠና እንደሚሰጡ፣ ኢንፍራስትራክቸር በተለይ ለአካል ጉዳተኞች በልዩ ሁኔታ ተይዞ መሰራት እንዳለበት፣ አቅም በፈቀደ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
" ነገር ግን የትራፊክ ግጭቱ ስታቲስቲክሱ ሲታይ በዓመት አዲስ አበባ ከተማ ብቻ 401 ሰው ይሞታል። በአመት 401 ሰው ይሞታል ማለት በቀን ከ1 ሰው በላይ ይሞታል ማለት ነው " ሲሉ ተናግረዋል።
" ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚፈጠረው ግጭት ደግሞ መቆጣጠር የሚቻል፤ በሰዎች ስህተት የሚፈጠር እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት "ብለዋል።
" አንድ ክርክር አለ የትራፊክ አደጋ ነው ወይስ ግጭት ነው? የሚል። ከ95 በመቶ በላይ በሰዎች ባህሪ ላይ ሰርተን ለውጥ ማምጣት፤ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የወጡ ህጎችን ማክበር የምንችል ከሆነ ግጭቶችን መቀነስ የምንችልበት እድል ሰፊ ስለሆነ አደጋ ተብሎ ሊያዙ የሚገባ አይደሉም የሚል መከራከሪያ ይነሳል " ነው ያሉት።
" እውነት ነው፤ አንደኛው በአዲስ አበባ ላይ የግጭት አደጋ ምክንያት ከፍተኛ ፍጥነት ነው። ከ47 በመቶ በላይ አሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ከፍጥነት ወሰን በላይ ነው የሚያሽከረክሩት " ብለው፣ " ስለዚህ አንድ አካል ጉዳተኛ ዜብራ መንገድ እያቋረጠ እያለ በፍጥነት የሚመጣ አሽከርካሪ ተሽከርካሪውን ተቆጣጥሮ ከአደጋው ሊታደገው አይችልም " ሲሉም ተናግረዋል።
በመዲናዋ በመኪና አደጋ ግጭት ጭምር በየጊዜው የበርካቶች ሕይወት እንደሚያልፍ፣ በተለይ ዓይነ ስውራን ደግሞ ለዚህ ተጋላጭ እንደሆኑ ይነገራል፤ ጥናት አድርጋችሁ ነበር? ማኀበሩ ባለው መረጃ መሠረት ስንት ዓይነ ስውራን በዚሁ አደጋ ሞተዋል? ስንልም የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማኀበርን ጠይቀናል።
የማበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ረታ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ምላሽ፣ " የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብቶች ቃል ኪዳን አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ዳታ ሊኖራቸው እንደሚገባ በመንግስታት ላይ ግልጽ የሆነ ግዴታ ይጥላል። ነገር ግን በመንግስት በኩል እንደዚህ አይነት የተደራጀ አሰራር የለም " ብለዋል።
" እንደ ኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማኅበር ከጥር 18 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ ብዙ የመኪና ሞት አደጋዎች መድረሳቸውን ያለን መረጃ ያሳያል (ይህ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚያጋጥሙትን የሚያካትት አይደለም)። አደጋው ከፍተኛ ነው ማለት እንችላለን " ብለዋል።
" በጥር 18/2016 ዓ/ም አንድ የሞት አደጋ ሁለት ከባድ የአካል ጉዳት፣ በመጋቢት ለሚኩራ አንድ የሞት አደጋ ደርሶ ነበር፣ በሚያዚያ ወርም የሞት አደጋ ደርሷል፣ በመስከረም 2017 ዓ/ም በዓይነ ስውራን ላይ የሞት አደጋ ደርሷል፤ በሚያዚያ 2017 ዓ/ም በኮየ ፈጬ አንድ የሞት አደጋ ተመዝግቧል። አደጋው ከፍ እያለ እንደሆነ ነው የሚያሳየው " ነው ያሉት።
የችግሩ ምክንያቶች ሁለት እንደሆኑ በጥናት መዳሰሱን ገልጸው፣ "አንደኛው የኢንፍራስትራክቸር ችግር፤ ሁለተኛ ደግሞ Unsafe የሆነ የአሽከርካሪዎች አነዳድ እንደሆነ በጥናቱ ተመልክቷል" ሲሉም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
ጋዜጠኛ ታደሰ ሚዛን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ጋዜጠኛ ታደሰ ሚዛን ለቀናት ህመም ላይ እንደነበረ የተነገረ ሲሆን ሀምሌ 2 ቀን 2017 ዓ/ም በአሜሪካ ሲያትል ከተማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከጋዜጠኝነት እስከ የዜናና ወቅታዊ መረጃ ዳይሬክተር በመሆን አገልግሏል።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን " #የሚዲያ_ዳሰሳ " በሚል ርእስ ሲያቀርበው በነበረው ትንታኔ በአድማጭ ተመልካቾች ዘንድ ይታወሳል።
ወደ አሜሪካ በመሄድም በPhD ተመርቋል።
ከትምህርቱ ጎን ለጎንም እስከ ህልፈቱ ድረስ TBS በተባለው የትግርኛ ቴሌቪዥን በአማርኛና በትግርኛ ቋንቋዎች ወቅታዊና የመዝናኛ ፕሮግራሞች ሲያቀርብ ነበር።
በ1963 ዓ/ም በትግራይ ውቕሮ ከተማ የተወለደው ጋዜጠኛ ታደሰ ሚዛን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነትን ኮሙዩኒኬሽንን ክፍል በዲግሪ ተመርቋል። በጋዜጠኝነት ሙያ ለረጅም አመታት ሰርቷል።
መረጃው የቲቢኤስ ቴሌቪዥን ነው።
@tikvahethiopia
ሴጅ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት
የሁለት ወር ሙሉ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ (Modern Accountancy) የክረምት
ስልጠና የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም ይጀመራል።
👉 ተግባርን ከንድፈ ሀሳብ ያስተሳሰረ ስልጠና
👉 መሠረታዊ አካውንቲንግ እና ኦዲት አሰራር፣ ሙሉ የአካውንቲንግ ሒሳብ አሰራር በፒስቺሪ ተደግፎ እና የግብር አያያዝ ትምህርቶችን አካቶ የሚሰጥ
☎️ 0906777799 / 0906777755
አድራሻ፦ ቁ.1: ፒያሣ ቸርችል ጎዳና ኤልያና ሆቴል 2ኛ ፎቅ እና ቁ.2: መገናኛ ታሜጋስ ህንፃ 2ኛ ፎቅ
Telegram: /channel/sagetraininginstitute
Tiktok: sage_training_institute" rel="nofollow">https://www.tiktok.com/@sage_training_institute
Linkedin: https://www.linkedin.com/company/sage-training-institute
" መንግስት ሁሉን አቀፍ እና አካታች ፖለቲካዊ ውይይት ማድረግ አለበት " - የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ ከአምስት አመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አካሄደ።
በዚህ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
የኦነግ በማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ምን አለ ?
- መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይት ያድርግ፤
- የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ካሉ አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮች ይፍታ፤
- የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ እና ነፃ እንዲሆን ይሁን ሲል መጠየቁን አቶ ለሚ ተናግረዋል ።
ፓርቲው ላለፉት አምስት አመታት በየደረጃው ያሉ አመራሮቹና አባላቶቹ በመታሰራቸው እንዲሁም ከዋናው ጅምሮ በዞን እና ወረዳዎች ያሉት ጽህፈት ቤቶቹ በመዘጋታቸው የፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማሳለፉን የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት አስታውሰዋል።
በፓርቲው በውስጥ የገጠሙትን ችግሮች እና ክፍተቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ኮሚቴ መዋቀሩንም አቶ ለሚ ገልፀዋል።
ፓርቲው በሀምሳ አመት የትግል ጉዞው ያስመዘገባቸው ድሎች እና ድክመቶች በዚህ ጉባኤው ይገመግማል ያሉት አቶ ለሚ የወደፊት የሰላማዊ ትግል አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ በቀጣይ ጉባኤው እያደረገ ያለው ሰላማዊ ትግል ፀንቶ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ለሚ " መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ዴሞክራሲን መለማመድ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘብ ከወዲሁ እናሳስባለን " ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ፎቶ፦ ፋይል
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ነቀምቴ
#TikvahEthiopiaFamliyNekemte
@tikvahethiopia
#Sidama
ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አዲስ ፖሊስ አዛዥ ተሹሟል።
የምስራቅ ሲዳማ ዞን ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ማቴዎስ የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሆነዉ ተሹመዋል።
በፀጥታ ዘርፉ ዉስጥ ሪፎርም ዉስጥ እንደሆነ በሚነገረው የሲዳማ ክልል ፖሊስ ተቋም ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በተፃፈ ደብዳቤ የምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ማቴዎስ ከዛሬ ሐምሌ 2/2017ዓ/ም ጀምሮ የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሆነዉ ተሹመዋል።
የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ኮማንደር መልካሙ አየለ በምን ምክንያት እንደተነሱ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
#TikvahEthiopiaFamilyHawassa
@tikvahethiopia
#AddisAbaba
የትምህርት ቤት ክፍያ !
20 በመቶ ትምህርት ቤቶች በ2018 የትምህርት ዘመን አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ላይ ከወላጆች ጋር አለመስማማታቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አሳውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቅርቡ ባጸደቀው የግል ትምህርት አገልግሎት ክፍያ አሰራር ስርአት ደንብ ቁጥር 194/2017 መሰረት በ2018 የትምህርት ዘመን አገልግሎት ክፍያ ላይ ከ ተማሪ ወላጅና አሳዳጊዎች ጋር ካልተስማሙ መንግስታዊ ካልሆኑ የትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት መካሄዱን የከተማው ትምህርት ቢሮ አሳውቋል።
በውይይት መርሃ ግብሩ ፦
- የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ፣
- የትምህርት እና ሥልጠና ባለሥልጣን ከፍተኛ አመራሮች
- የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር ፣
- የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች እና የተማሪ ወላጅ ኮሚቴ ተወካዮች እንደ ተሳተፉ ቢሮው በማህበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል።
ውይይቱ የተካሄደው በጭማሪው ላይ መስማማት ላይ ያልደረሱ ትምህርት ቤቶች ደንቡ በሚያስቀምጠው መሰረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ውሳኔ ያሳለፈ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ አስተሳሰብ ለመያዝ እንዲቻል መሆኑን ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ "በደንቡ መሰረት 80 ፐርሰንት ያህል ትምህርት ቤቶች ከወላጆችና አሳዳጊዎች ጋር በመስማማት የአገልግሎት ክፍያ መጨመራቸው የሚበረታታ ተግባር ነው" ብለዋል።
እንደ ትምህርት ቢሮ ሃላፊው ገለጻ 20 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከክፍያ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ከወላጆች እና አሳዳጊዎች መስማማት ላይ አለመድረሳቸውን አመላክቷል።
የትምህርትና ስልጠናና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢዘዲን ሙስባህ "በደንቡ ላይ በመግባባት ወደ ስራ መገባቱን በዚህም መሰረት በርካታ ትምህርት ቤቶች ከወላጆች ጋር በመስማማት መጨመራቸውን ፣ መመሪያውን መሰረት በማድረግም ባለስልጣኑ በተቀሩትና መስማማት ባልቻሉት ላይ ውሳኔ መስጠቱን" አሳውቀዋል ።
ባለሥልጣኑ ምን ውሳኔ እንዳሳለፈ በዝርዝር ባይገለጽም የወላጆችን የመክፈል አቅም እና የትምህርት ተቋማቱን የግብአት አቅርቦት ታሳቢ አድርጎ ተግባራዊ የሆነ መሆኑን ስለመናገራቸው ትምህርት ቢሮው አሳውቋል።
#AddisAbabaEducationBureau
@tikvahethiopia
" መንግስት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የመዝጋትም ሆነ የማዳከም ፍላጎት የለውም " - የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን፣ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተዋናዮች በዳግመ ምዝገባው ዙርያ ላቀረቡት ቅሬታ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ፣ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃለመጠይቅ፣ መንግስት ተቋማቱን የማጥፋት እቅድ አለው እየተባለ ለሚቀርበው ቅሬታ በሰጡት አስተያየት፣ " ይሔ አስተያየት ስህተት ነው፣ እነዚህን ተቋማት የማዳከም አላማ የለም " ብለዋል፡፡
" ይልቁንም መንግስት እነዚህን ተቋማት የማጠናከር አላማና ፍላጎት ነው ያለው፣ የዳግመ ምዝገባና ምዘና ሒደቱ ትኩረትም ይህን እውን ማድረግ ነው " ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የዳግመ ምዝገባና ምልከታ ሒደቱ በአዲስ አበባ መጠናቀቁን ተናግረው፣ በቀጣይ የትኞቹ ተቋማት ይቀጥላሉ፣ የትኞቹ አይቀጥሉም የሚለውን ለመግለፅ ሪፖርት በመዘጋጀት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የአዲስ አበባው የዳግመ ምዝገባና ምዘና ስራ በመጠናቀቁ፣ በቅርቡ በክልሎች ይህንን ስራ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ውብሸት ታደለ በዝርዝር ምን አሉ ?
" አሁን እየተከናወነ ባለው ዳግመ ምዝገባና ምዘነና ሒደት የተፈለገው፣ የትምህርት ተቋማቱ መሰረታዊ በሆነ መንገድ ራሳቸውን እንዲያድሱ ነው፡፡
ባለቤትነታቸው እንኳ የማይታወቅና አጠራጣሪ የሆኑ ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች የማጥራት ስራ ነው እየተሰራ ያነው፡፡መዝጋት የምትፈልገውን ተቋም ይህን ያህል ጊዜ ማቆየት አያስፈልግም፡፡ በፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጠህ ከገበያ እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል፡፡ ግን እሱ አይደለም አላማችን፡፡
የእኛ አላማ፣ ትናንሽ ቢዝነሶች ሆነው የጀመሩት ተቋማት ወደ አንድ ተደራጅተውና ተጠናክረው እንዲመጡ ነው፡፡ ካልቻሉ ደግሞ ከገበያው መውጣት አለባቸው፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ (ፕሮፌሰር ብረሀኑ ነጋ) ከዚህ በፊት የተናገሩት ነገርም (50 ተቋማት ይበቃሉ ማለታቸው ይታወሳል) ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ጠንከር ጠንከር ያላችሁ ተቋማት ሁኑ፡፡ ጥቂት ተቋማት ይበቃሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተቋም አለ ማለት፣ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተለየ ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም ነው ያሉት፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጥ ተቋም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ የእኛም አላማ ይኸው ነው፡፡
ከዚህ በፊት ወጣ የተባለው፣ ' አብዛኞቹ ተቋማት መስፈርቱን አያሟሉም ተብለዋል ' የተባለው ዘገባ ስህተት ነው፡፡ ሚድያዎችን ለመተባበር ብለን የሰጠናቸውን መረጃ አዛብተው ዘገቡት፡፡ ከዛም፣ ሁሉም የግል ትምህርት ተቋማት መስፈርቱን አያሟሉም ተባለ ተብሎ ተስተጋባ፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡
በወቅቱ ያልነው፣ አብዛኞቹ ተቋማት ለዳግመ ምዝገባ የሚሆን የተሟላ ሰነድ አላቀረቡም ነው፡፡ ሰነድ አስገቡ ስንላቻው ስለነበር ማለት ነው፡፡ ሰነድ አላሟሉም ማለትና ያስገቡትን ሰነድ ገምግሞ መስፈርቱን አላሟሉም ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡
ቀደም ሲል ሒደቱ በጣም ቀላል ነበር ኮሌጅ ለመክፈት፣ ትንሽ ገንዘብ ካለህ አንድ ሁለት ክፍል ተከራይተህ መክፈት ነበር፡፡ በዚህ መሰሉ ሒደት መቀጠል አይቻልም አሁን፡፡ ይህን ቀላል አካሔድ የለመዱ ተቋማት መቀጠል አይችሉም፡፡ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው በትንሹ ኮሌጅ የሚያስብል ስራ ሰርተው ነው ይህንን ቢዝነስ መጀመርና ማስኬድ ያለባቸው፡፡
አሁን በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በተቀመጠው መስፈርት መሰረት እንደ ኮሌጅ መቀጠል እችላለሁ የሚሉት ተቋማት ናቸው የተመዘገቡት፡፡ ከተመዘገቡት መካከል ደግሞ፣ አሁን ግምገማ ተደርጎ፣ ሰነዶቻቸው ተፈትሸው፣ የመስክ ምልከታም ተደርጎ፣ በትክክል መስፈርቱን ያሟላሉ የሚባሉትን ውጤት እንገልፃለን፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የአዲስ አበባን ተቋማት ምዝገባና ምልከታ ሙሉ በሙሉ አጠናቀናል፡፡ ውጤቱን ለመግለፅ ሪፖርቱን በማዘጋጀት ላይ ነው ያለነው፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ በክልሎች ይህንን ስራ ለመጀመር ቅድመ ዘግጅት እያደረግን ነው፡፡ ስራው በአዲሱ የበጀት አመት የሚጀመር ይሆናል፡፡
እስካሁን ከዘርፉ የወጡ ተቋማትን በተመለከተ የተለያየ አሀዝ ይቀርባል፡፡ ለምሳሌ መጀመሪያ ላይ 84 ተቋማት ሳይመዘገቡ ቀሩ፡፡ በኋላ ላይ ግን ዘግይተው የመጡ አሉ፡፡ ከነሱ ውስጥ በቂ ምክንያት ያቀረቡትን መዝግበን እየገመገምን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተመዝግበው ከነበሩት ውስጥ ለመውጣት ሒደት ላይ ያሉ አሉ፣ ጎንለጎን ማለት ነው፡፡ ይህ የእነሱ ገባ ወጣ ማለት፣ ከዘርፉ የወጡ ተቋማት ብዛት በየጊዜው እንዲለያይ አድርጎታል፡፡ እንደዛም ሆኖ፣ አሁን የምዝገባና የግምገማ ሒደት ላይ ስለሆንን ትክክለኛ ቁጥሩን ማስቀመጥ ቢያስቸግርም ቢያንስ 80 የግል ትምህርት ተቋማት፣ ስራቸውን አቋርጠው ከዘርፉ ተሰናብተዋል፡፡
የዳግመ ምዝገባው መመሪያ ላይ በቂ ውይይት አልተደረገበትም፣ ከዘርፉ ተዋናዮች ግብአት አልተወሰደም የሚለውም ጉዳይ ትክክል አይደለም፡፡ ከተቋማቱ ባለቤቶች በሁለት መንገድ ግብአት ተቀብለናል፡፡ አንደኛው፣ ከውይይት መድረክ የተገኘው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በፅሑፍ የተቀበልነው ነው፡፡ በዚህ መንገድ በአዲስ አበባ በሀይሌ ግራንድ ሆቴል ከተደረገ ውይይትና በፅሑፍ ከቀረቡልን ሀሳቦች ግብአት ወስደናል፡፡አስፈላጊ የሆኑትንና ያስኬዳሉ የምንላቸውን ሀሳቦች በግብአትነት ተጠቅመንባቸዋል፡፡
ለምሳሌ ፦ ከእነሱ ተቀብለን ካካተትናቸው ሀሳቦች አንዱ፣ በመውጫ ፈተና ቢያንስ 25 በመቶ ያላሳለፈ ተቋም መቀጠል የለበትም የሚለው መስፈርት መቼ ተግባራዊ መሆን ይጀምር የሚለው ላይ የእነሱን ሀሳብ ተቀብለን የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጥ አድርገናል፡፡
ይህ መስፈርት መተግበር የሚጀምረው፣ መመሪያው በወጣበት ጊዜ ትምህርት በጀመሩ ተማሪዎች ላይ እንጂ፣ በነባር ተማሪዎች ላይ መሆን የለበትም የሚለው ሀሳብ ከነሱ የመጣ ነው፡፡ ይህ ሀሳባቸው አሳማኝ በመሆኑ ተቀበልነው፡፡ አሁን ለትግበራው ሁለት አመት ገደማ አላቸው፡፡ በ 2019 ዓ.ም ገደማ ነው መተግበር የሚጀምረው ይህ መመሪያ፡፡ ሌሎችም የተቀበልናቸው ሀሳቦች አሉ፡ " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#AAiT
Announcement of Professional Training Programs
Python Programming + Data Analytics and Visualization
By: Addis Ababa University,
College of Technology and Built Environment,
School of Electrical & Computer Engineering
Registration Deadline: July 24, 2025
Training Starts on: July 26, 2025
Online Registration Link: https://forms.gle/M1DPS1zFP4K9QT4V6
Telephone: +251-913-574525/ +251-940-182870
Email: sece.training@aait.edu.et
For more information: https://forms.gle/M1DPS1zFP4K9QT4V6
Telegram Channel: /channel/TrainingAAiT
#AddisAbaba
" በዘንድሮ የግብር ማሳወቂያ እና መክፈያ ወቅት በገቢዎች ቢሮ 256 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል " - ገቢዎች ቢሮ
ከሐምሌ 1/2017 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30/2018 ዓ/ም ድረስ የ2017 ዓ/ም የግብር ማሳወቂያ ወቅት ነው።
በዛሬው ዕለት የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋይ ደንበኞች ግብራቸውን ማሳወቅ የጀመሩ ሲሆን እስከ ሐምሌ 30/2017 ዓም ድረስ ግብር ግብራቸውን እያሳወቁ ይቆያሉ።
ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር ለየት ባለ መልኩ በየደረጃው ያሉ ግብር ከፋዮች በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት ግብራቸውን እንዲከፍሉ እንደሚደረግ የቢሮው የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
አቶ ሰውነት " ከዚህ ቀደም የደረጃ 'ለ' ግብር ከፋዮች ከሃምሌ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ነበር የሚከፍሉት ዘንድሮ ይህ አሰራር ተቀይሮ ሃምሌን ለዝግጅት እንዲጠቀሙት እና ግብራቸውን ከ ነሐሴ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ እንዲከፍሉ ተወስኗል አከፋፈላቸውም በስም ቅደም ተከተል ይሆናል " ብለዋል።
ዳይሬክተሩ በስም ቅደም ተከተል እንዲከፍሉ መደረጉ ግብር ከፋዩ ላይ መጨናነቆች እንዳይኖሩ እና ለብልሹ አሰራሮች እንዳይዳረጉ ያግዛል ነው ያሉት።
አቶ ሰውነት አየለ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በዝርዝር በሰጡት ሃሳብ ምን አሉ ?
" የደረጃ 'ለ' ግብር ከፋይ ደንበኞች በነሐሴ ወር የመጀመሪያው ሳምንት ላይ የስም ዝርዝራቸው ከ A-D ያሉ ግብር ከፋዮች የሚስተናገዱበት ፕሮግራም ወጥቷል፣ በዚህም መሰረት ግብር ከፋዩን በአራት ሳምንት በመከፋፈል አመታዊ ግብራቸውን እንዲያሳውቁ እና እንዲከፍሉ ይደረጋል።
የደረጃ 'ሀ' ግብር ከፋዮችን በሚመለከትም ከዚህ ቀደም ከሐምሌ 1 እስከ ጥቅምት 30 የአመታዊ ግብራቸውን የመክፈያ እና የማሳወቂያ ጊዜያቸው ነበር።
እነዚህ ግብር ከፋዮችም ሐምሌ እና ነሃሴን ለዝግጅት ተጠቅመው መስከረም እና ጥቅምትን ግብራቸውን የሚከፍሉበት ፕሮግራም ወጥቷል።
ቢሮው በተለያዩ ጊዜያት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች ወቅት የተነሱ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ እነዚህን የተጠቀሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ በጥናት የተለዩ 24 አይነት አዳዲስ አሰራሮችን ዘርግተናል ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።
ለምሳሌ የኦዲት ጥራት ጋር ላይ ከአሰራር ጋር በተያያዘ ባሉ ክፍተቶች ምክንያት ሁለት ኦዲተሮች አንድ አይነት ፋይል ተመልክተው ውሳኔ ሲወስኑ ግን ሁለት አይነት ውሳኔ የሚወስኑበት አሰራር ነበር ይህንን ለማስቀረት የሚያስችል የአሰራር ስርአት ተዘርግቷል።
ከሂሳብ መዝገብ ጋር በተገናኘም የሂሳም መዝገብ መያዝ ያለባቸው ግብር ከፋዮች መዝገቡን ባለመያዛቸው በቁርጥ ግብር ሲስተናገዱ ነበር።
አፈጻጸም ላይ በነበረ ክፍተት ምክንያት በተለይም የደረጃ 'ሀ' እና 'ለ' ግብር ከፋዮች ያለ ሂሳብ መዝገብ ሲስተናገዱ የቆዩ ቢሆንም ከአሁኑ የ2017 ዓ/ም የግብር ማሳወቂያ ወቅት ጀምሮ ያለ ሂሳብ መዝገብ አይሰራም።
ሂሳብ መዝገብ ሳይዙ የሚመጡ ከሆነ ግን የሚወሰነው ውሳኔ አስተማሪ የሚሆን ይሆናል።
የግብር አሰባሰብ ስርአቱም ከእጅ ንክኪ በጸዳ መንገድ እንዲሆን በማሰብ የደረጃ 'ሐ' ግብር ከፋዮች በET-TAX በተሰኘ በተቋሙ በለማ መተግበሪያ እቤታቸው ተቀምጠው ግብራቸውን የሚያውቁበት እና የሚከፍሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በSMS በሚደርሳቸው መረጃም በTelebirr እና CBE Birr ግብራቸውን መክፈል ይችላሉ።
የደረጃ 'ሀ' እና የደረጃ 'ለ' ግብር ከፋዮችም በተመሳሳይ E-TAX በተሰኘ መተግበሪያ እንዲከፍሉ እያደረግን ያለንበት ሁኔታ አለ ነገር ግን ሁሉም ወደዚህ አሰራር ስርአት ገና አልገቡም።
ከፍተኛ ግብር ከፋዮች 100 ፕርሰንት ወደዚህ አሰራር ስርአት ገብተዋል ቀሪዎቹ በየቅርንጫፉ እቅድ ተይዞ አብዛኛው ግብር ከፋይ ወደዚህ አሰራር እንዲገባ እየተሰራ ነው።
የኦዲት ጥራትን የሚያረጋግጥ የስራ ክፍል ተደራጅቷል ኦዲተሩ የወሰነው ውሳኔ ምን ያህል ጥራት አለው የሚለውን ያረጋግጣል ከፍተኛ ልዩነት ከተፈጠረም ግብር ከፋዩ እንዲከፈል ይደረጋል፣ ይህንን የወሰነው አካልም ተጠያቂ ይሆናል።
የግብር ከፋዩን ሂሳብ መዝግብ የሚያዘጋጁ ባለሞያዎች በሚመለከት ከዚህ ቀደም ከግብር ከፋዩ ጋር በመደራደር ከፍተኛ የሆነ ግብር የመሰወር ስራ የሚሰሩበት እና የተሳሳቱ ሰነዶችን የሚያቀርቡበት ሁኔታ ነበር።
በዚህ ጊዜ ግብር ከፋዩን ኦዲት አድርገን ገንዘቡን ብናስከፍልም የሂሳብ ባለሞያዎቹ ተጠያቂ የምናደርግበት አሰራር አልነበረም አሁን የሂሳብ ባለሞያዎቹም ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር ዘርግተናል።
ኦንላይን ግብይትንም ለመቆጣጠር እና ግብር እንዲከፍሉ ለማድረግ የሚቻልበት የአሰራር ስረዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው።
ከማዕከል ሁሉንም ቅርንጫፎች ለመቆጣጠር የሚያስችል ካሜራ አስገጥመናል።
በዘንድሮ የግብር ማሳወቂያ እና መክፈያ ወቅት በገቢዎች ቢሮ 256 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAddisAbaba
@tikvahethiopia
#Ethiopia🇪🇹
አስገዳጅ የቦንድ ግዢ መመሪያው መነሳቱ ለባንኮች ምን ትርጉም አለው ?
ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ባካሔደው ሶስተኛ ስብሰባ፣ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹ አንዱም የንግድ ባንኮች ሲገዙት ከነበረው የግምጃ ቤት ቦንድ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡
ኮሚቴው፣ የንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ የግምጃ ቤት ቦንድ እንዲገዙ የሚያስገድደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ እንዲነሳ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ይህም የሆነው በአሁኑ ወቅት የመንግስት ገቢ የማሰባሰብ አቅም በእጅጉ በመሻሻሉና መንግስት የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት የውጭና ገበያ መር ከሆኑ የሀገር ውስጥ የመበደሪያ አማራጮችን እየተጠቀመ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡
የንግድ ባንኮች ቦንድ እንዲገዙ ሲደርግ የነበረው አስገዳጅ መመሪያ በመነሳቱ፣ ለባንኮቹ ምን ፋይዳ አለው ? በማለት ቲክቫህ ኢትዮጵያ የጠየቃቸው አንድ ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ፣ " አሰራሩ በባንኮች ዘንድ የገንዘብ እጥረት እንዲፈጠር አስተዋፅኦ ስለነበረው፣ ይህ ውሳኔ በጣም ጠቃሚ ነው " ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የባንክ ባለሙያው በዝርዝር ምን አሉ ?
" ቦንዱ እንኳን ተነሳ፡፡ በቦንዱ ምክንያት ለአምስት አመት ታስሮ የሚቀመጥ ገንዘብ ነበር፡፡ ባንኮቹ ቦንድ የገዙበት ገንዘብ ከአምስት አመት በኋላ ነው የሚመለስላቸው፡፡
ይህ አስገዳጅ የቦንድ ግዢ መመሪያ፣ በባንኮች የገንዘብ እጥረት/የሊኩዲቲ ችግር እንዲመጣ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ለሊኩዲቲ ችግር መከሰት አንዱ መንስኤ የነበረው እሱ ነው፡፡
የሆነ ብድር በሰጠህ ቁጥር የተወሰነ ፐርሰንት ቦንድ እድትገዛ ትገደድ ነበር፡፡ ብድር በሰጠህ ቁጥር የብድሩን 20 በመቶ ቦንድ ግዛ ትባላለህ፡፡ እስከ 20 በመቶ እንድተገዛ ትገደድ ነበር፡፡ ለአንድ ሰው አምስት ጊዜ ካበደርክ ያስቀመጥከውን ገንዘብ በሙሉ ወሰደው ማለት ነው የቦንድ ግዢው፡፡ በዚህ መልኩ ባንኮች ብድር በሰጡ ቁጥር ተደራራቢ የቦንድ ግዢ ስለሚፈፅሙ እና ገንዘቡም የሚመለሰው ከአምስት አመት በኋላ ስለነበረ ለገንዘብ እጥረት አጋልጧቸዋል።
አሁን ይኼ በመቆሙ ትልቅ እፎይታ ነው የሚሰጣቸው፡፡ ለችግራቸው መፍትሔ ይሆናል፡፡ ለገንዘብ እጥረቱ ማስተንፈሻ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ በእጅጉ አጋዥ ነው፣ የሚያስመሰግነው ነው፡፡
በቦንድ ግዢ ከባንኮች ሲሔድ የነበረው የገንዘብ መጠን፣ ባንኮቹ በሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የሚመሰረት ነበር፡፡ አሁን ይሔ አሰገዳጅ የቦንድ ግዢ መመሪያ በመቅረቱ፣ የባንኮቹን የገንዘብ እጥረት በምን ያህል መጠን ሊያቃልለው እንደሚችል ማወቅ ይከብዳል፣ ግን በእጅጉ ያቃልላል፡፡
ይሔ ጥሩ እርምጃ ሆኖ፣ የንግድ ባንኮች የሚሰጡት ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያ ደግሞ አልተነሳም፡፡ ከ18 በመቶ እንዳይበልጥ የተቀመጠው የብድር ጣሪያ እስከ መስከረም ወር እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በዚሁ እርምጃው ይህንንም 18 በመቶ የሚለውን የብድር ጣሪያ ቶሎ ቢያነሳው ጥሩ ነበር፡፡
የብድር ጣሪያው በባንኮች አሰራር ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ያለው፡፡ ለምን ብትል ተበዳሪዎች ብድራቸውን ከመለሱ በኋላ በባንኮች ላይ በተጣለው የብድር ጣሪያ ምክንያት መልሰው እንደማይበደሩ ስለሚያውቁ የመጀመሪያውንም ብድራቸውን አይከፍሉም፡፡ ለባንክ የሚከፍሉትን እዳ ለሌላ አገልግሎት ያውሉታል፡፡
ይልቁንም ለባንክ መክፈል የነበረባቸውን ገንዘብ ለሌላ ንግድ እያገላበጡ ይጠቀሙበታል፡፡ ለዚህ ነው እዳ ውስጥ የሚገቡት፡፡ ባንኮቹ በተቀመጠው የ 18 በመቶ የብድር ጣሪያ ምክንያት ተጨማሪ ብድር መስጠት አይችሉም ብቻ ሳይሆን ቀድመው ያበደሩትን ገንዘብ ማስመለስ አልቻሉም፡፡
ብሔራዊ ባንክ ይህንን የብድር ጣሪያ የሚያነሳበትን ጊዜ በጉጉት ነው የምንጠብቀው፡፡ እርምጃው ለኢንቨስትመንትና ለስራ ፈጠራም አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ የግሉ ዘርፍ ከባንኮች እየተበደረ ኢንቨስት ካላደረገ ኢኮኖሚው አይንቀሳቀስም፣ የስራ እድል ሊፈጠር አይችልም፣ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው ብዙ ነው፡፡ " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#NationalExam🇪🇹
#SocialScience
የ2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል የማኀበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የመጀመሪያ ዙር ፈተና ዛሬ ከጥዋት ጀምሮ መሰጠት ተጀምሯል።
በወረቀት እና በኦንላይን የሚሰጠው የማኀበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተና እስከ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም ይቆያል።
@tikvahethiopia
#AcademicCalendar
በመዲናዋ ለ2018 የትምህርት ዘመን የነባር እና አዲስ ተማሪዎች ምዝገባ እንዲሁም የመፀሀፍ ስርጭት የሚካሄደው ከሐምሌ 1 እስከ ነሃሴ 23/2017 ዓ/ም መሆኑ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ/ም የትምህርት ቀናትን ዛሬ ይፋ አድርጓል ለ11ዱም ክ/ከተማ የትምህርት ፅ/ቤቶች ልኳል።
በዚሁ ካላንደር መሰረት ምዝገባ ከሃምሌ 1 እስከ ነሔሴ 23 /2017 ዓ/ም ይካሄዳል።
መምህራን በትምህርት ቤታቸው ተገኝተው ሪፖርት የሚያደርጉበት እንዲሁም አጠቃላይ የመምህራን ጉባኤ የሚደረገው ነሃሴ 28 እና ነሃሴ 29/2017 ዓ/ም እንደሆነ ተመላክቷል።
ከነሃሴ 24 እስከ ጳጉሜ 5/2017 ዓ/ም ደግሞ የ7ኛና የ9ኛ ክፍል ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚመጡ አዲስ ተመዝጋቢዎች ተማሪዎች ምዝገባ ይከናወናል።
መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ/ም የመጀመሪያው ቀን የመጀመሪያ መደበኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜ (day one class one) እንደሆነ ይፋ ተደርጓል።
በ2018 ዓ/ም የሚሰጠው የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ የአንደኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና እንደሚሰጥ በትምህርት ካላንደሩ ላይ ታሳቢ ተደርጓል።
(ሙሉውን ከላይ ይመለከቱ)
@tikvahethiopia
" ቡድኑ ትግራይን ለማተራመስና ኢትዮጵያን ለመውጋት ከኤርትራ መንግስት ጋር እየሰራ ነው " - ስምረት ፓርቲ
የኢፌዴሪ መንግስት ከኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ የተሰረዘው ' #ህወሓት ' ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንጂ ማስታመም አይገባውም አለ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ።
በቀድሞ የህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበርና የትግል ጓደኞቻቸው በቅርቡ ከብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የቅድመ እውቅና ምዝገባ የተሰጠው ስምረት " ለህግ የማይገዛ ወመኔ " ሲል የገለፀው ህወሓት ትግራይን ለማተራመስና ኢትዮጵያ ለመውጋት ከኤርትራ መንግስት እየሰራ ነው " ሲል ከሶታል።
" ኋላ ቀር ቡድን " በማለት በገለፀው ህወሓት ምክንያት የትግራይ ህዝብ መልሶ ወደ ጦርነት እንዳይገባ የፌደራል መንግስት ሃላፊነቱ እንዲወጣ አሳስቧል።
" ከአሁን በኋላ በትግራይ ላይ የሚፈፀሙ ጥፋቶች ብቸኛው ተጠያቂ ከዓለም አቀፍና አገራዊ ህጎች የተቃረነው ወመኔው ኋላ ቀር ቡድን እና መሰሎቹ መሆናቸው የኢትዮጵያ መንግስት መገንዘብ አለበት " ሲልም ስምረት ፓርቲ ገልጿል።
" የሃይማኖት አባቶች ፣ የአገር ሽማግሌዎች ፣ ወጣቶች በአገር ውስጥና በመላ ዓለም የሚገኙ ትግራዎት ቡድኑ በስልጣን የሚቆይባቸው እያንዳንዱ ቀናት በህዝብ ላይ አስከፊ መከራና ስቃይ የሚያስከትሉ መሆናቸው በመረዳት ትግላችሁ አጠናክሩ " ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ፓርቲው ለታጠቀው ሰራዊት ባስተላለፈው ጥሪ " ሌት ተቀን የጦርነት ነጋሪት ከሚጎስመው ኋላ ቀር ቡድን ራሳችሁን በማራቅ ከሰላም ፈላጊ ህዝብ ጎን ተሰለፉ " ብሏል።
" ከአሁን በኋላ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈፀም ወንጅልም ይሁን የሚቀሰቀስ ጦርነት በዝምታ ማየት በህዝብ ላይ የሚያስከትለው ከባድ አደጋ መዘንጋት ነው " ያለው ስምረት ፓርቲ " አደጋውን አስቀድሞ ለማስቀረት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ሚናቸው ከወዲሁ እንዲወጡ " በማለት ለአገር አቀፍና ዓለምአቀፍ ተቋማት ጥሪውን አቅርቧል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
#TikvahEthiopiaFamilyMekelle
@tikvahethiopia
#SafaricomEthiopia
አሁንም በSMS ጨዋታ ፈታ💬🎊 እያልን በየቀኑ እንሸለም! 🎁
ከሳፋሪኮም ቁጥራችን 'START’ ብለን ወደ 34000 በመላክ ወይም ወደ *799# በመደወል እንወዳደር! እናሸንፍ! በአንድ መልስ 1ብር ብቻ!
#1Wedefit
#Furtheraheadtogether
#Ethiopia🇪🇹
የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ በሚቀጥለው ሳምንት ይፋዊ ግብይት ሊጀምር እንደሆነ ካፒታል ጋዜጣ አስነብቧል።
ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ( ስቶክ ገበያ) በሚቀጥለው ሳምንት ሥራ ሊጀምር መሆኑ ተሰምቷል።
ይህ እርምጃ ለአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ ተነግሯል።
ገበያዉ በኖቬምበር 2023 በተደረገ የካፒታል ማሰባሰቢያ ዘመቻ 1.5 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ ከታሰበው ግብ በ631% በልጧል። ይህ ገንዘብ ከ48 የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተገኘ ነው።
በሕዝብና በግል ሽርክና የሚሰራው አዲሱ የበይነመረብ ንግድ ልዉዉጥ መድረክን መንግሥት 25%፣ የግል ዘርፍ ደግሞ 75% ድርሻ አላቸዉ።
አሁን ላይ ገዳ ባንክ አ.ማ. እና ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አ.ማ. በገበያው ላይ ከተመዘገቡት ኩባንያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የሰነደ መዋዕለ ንዋይ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ እስከ 50 ኩባንያዎችን፣ በአሥር ዓመታት ውስጥ ደግሞ ከ90 በላይ ንግዶችን ለማካተት አቅዷል።
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የካፒታል ጋዜጣ ነው።
@tikvahethiopia
" የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ድምጽ አልባ በመሆናቸው ራሳቸውን በድምጽ ከአደጋ የሚከላከሉ በተለይም ዓይነ ስውርና መስማት የተሳናቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ትልቅ አደጋ ላይ ናቸው " - ማኅበሩ
የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማኅበር ከአዲስ አበባ ብስራት ፕሮሞሽን ጋር በማበር፣ የመንገድ ላይ ደኅንነትን፣ የትራንስራንስፓርት ተሽከርካሪዎች እና የአገልገሎት መስጫ ተቋማት ተደራሽነት ችግር አካቶ የያዘ "ከቤት እስከ ጎዳና" በሚል ያዘጋጀውን ዶክመንትሪ ፊልም ለመንግስት አካላት በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል አቅርቧል።
በዚህም የትራንስፖርትና ሎጂስቲ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንትና ሌሎች ተቋማት ታድመው የነበረ ሲሆን፣ ማኀበሩም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናታዊ ፅሑፍ ጭምር እነዚሁ አካላት ባሉበት አቅርቧል። ባለድርሻ አካላቱም የተለያዩ አስተያየቶችን በመስጠት የተነሱትን ክፍተቶች ለመቅረፍ ቃል ገብተዋል።
በመርሃ ግብሩ የተነሳው አንዱ ዋነኛ ጉዳይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተለይ ለዓይነ ስውራን አደጋ የደቀኑ በመሆናቸው ሕግና ፓሊሲ በማውጣት መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ የሚያሳስብ የነበረ ሲሆን፣ ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባት በዓይነ ስውራን የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው? ምንስ መደረግ አለበት? ያለው ክፍተትስ ምንድን ነው? ሲል ማህበሩን ጠይቋል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ረታ ምን መለሱ ?
" መንግስት በጣም የሚደነግበት ቦታ ቢኖር እዚህ ኤሪያ ላይ ነው፡፡ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር ይሄንን ጉዳይ ስናወራቸው ምንም ያላሰቡበት ነገር እንደሆነ ነው የነገሩን።
የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ድምጽ አላባ/ድመጽ አልባ አድርጎ መንዳት የሚችሉ ናቸው፡፡ ይሄ ሲሆን ግን እይታ የሌላቸው ነገር ግን ራሳቸውን በድምጽ ከአደጋ የሚከላከሉ በተለይም ዓይነ ስውርና መስማት የተሳናቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ትልቅ አደጋ ላይ ናቸው።
መንግስት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመቀየር እቅድ ይዟል። ይሄንን እቅድ ሲይዝ ግን ቀጥታ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑትን ዓይነ ስውራንን ያገናዘበው ፖሊሲም፣ ሕግም ስታንዳርድም የለም፡፡ ይሄ ጉዳይ በአሜሪካ ምክር ቤት ክርክር ተደርጎበት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሙሉ ለሙሉ ድምጽ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገዳጅ ሕግ ወጥቶለታል።
በኢትዮጵያ ግን ለነዳጅ የምናወጣውን የውጭ ምንዛሬ ስለሚያስቀርልን፣ ኢንቫይሮመንታሊ ፍሬንድ ስለሆኑ በሚል እሳቤ ተሸከርካሪዎቹን ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባናቸው ነው።
መግባቱን ይግቡ ግን ቴክኖሎጅው ሁሉም ነገር የተገጠመለት ነው፤ ነገር ግን እኛ ጋር የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ስለሌለ ዝም ብለን አስገብተን በመንገድ ላይ ጥቅም እንዲሰጡ እያደረግናቸው ነው ያለነው፡፡ ይህ ለዓይነ ስውራን አደገኛ የሆነ አካሄድ ስለሆነ መንግስት ሊያስብበት ይገባል፡፡
ምክንያቱም ተሽከርካሪዎቹ ድምጽ ስለሌላቸው መጥተው ሲገጩን ብቻ ነው የምናውቀው፡፡ አንድ ዓይነ ስውር በሚጓዝበት ወቅት አደጋ መኖርና አለመኖሩን የሚለየው ድምጽ በመስማትና በነጭ ብትሩ በመዳበስ ነው" ብለዋል።
በአጠቃላይ በዘርፉ ስላለው ችግር ሲያስረዱም፣ "የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎቹ ድምጽ ስለሌላቸው ዓይነ ስውራን ራሱ ቢገቡባቸውና/ቢጋጩ የአሽከርካሪዎች ኃላፊነት ከፍተኛ ድርሻ ስለሚይዝ ሊጣል የሚገባው ካሳ ሊቀንስልኝ ይገባል በሚል ክርክር ውሳኔው ምንድን ነው? በሚለው ዙሪያ በዓይነ ስውራን ወገኖች ረገድ ሕግ የለም " ነው ያሉት።
የመፍትሄውን ሃሳብ በተመለከተ ለጊዜው መንግስት በዚሁ ረገድ ሰርኩላር በትኖ የቁጥጥር ስልቱን መንደፍና መተግበር፣ በዘላቂነትም የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በተመለከተ ሕግና ፖሊሲ እንዲያወጣም አሳስበዋል፡፡
(ተጨማሪ አለን በቀጣይ ይቀርባል)
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia