#AddisAbaba #ባጃጅ
በአዲስ አበባ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት በሂደት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ አይቀሬ እንደሆነ ተሰምቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ የባለሶስት እና አራት እግር ተሽከርካሪ ወይም ባጃጅ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የአሰራር ፣ የአጀረጃጀት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የዲሲፒሊን ቁጥጥር አፈጻጸም መመሪያ ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጎ ነበር።
በውይይቱ ላይ ፦
- የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ
- የትራፊክ ማናጅመንት ፣
- የትራንስፖርት ቢሮ
- የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማዕከልና የክ/ከተሞች ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር።
በአፈፃፀም መመሪያው የባለ ሶስትና አራት እግር ተሽከርካሪ ወይም ባጃጅ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ካሁን ቀደም ሲያጋጥሙ የነበሩ የሕግ ጥሰቶችንና የደንብ መተላለፎችን ለመከላከል ሲባል አገልግሎት ሰጪዎቹ ፦
☑ የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ፣
☑ የአዲስ አበባ የሠሌዳ ቁጥር
☑ በማህበር መደራጀት እንደሚኖርባቸው ተገልጿል።
" በአዲስ አበባ፣ የከተማ አስተዳደሩን ታርጋ ለጥፈውና የአዲስ አበባ መታወቂያ ይዘው ከሚሰሩት ይልቅ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አሽከርካሪዎች መበራከት የፀጥታ ችግር ሆነው ቆይተዋል " ተብሏል።
ይህ ደግሞ በተለይ በወንጀል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች እንደነበር ተገልጿል።
በዚሁ መድረክ ላይ " የባጃጅ ትራንስፖርት የከተማዋን ዘመናዊ እሳቤ የሚመጥን ስላልሆነ በሂደት ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱ የሚቋረጥ ይሆናል " ተብሏል።
" እስከዚያ ጊዜ ድረስ የባለሶስት እግር አሽከርካሪዎች የአዲስ አበባ መታወቂያ፣ ታርጋ እና በማህበር መደራጀት ይኖርባቸዋል " ነው የተባለው።
አሁን ላይ በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ሰፊ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት በመኖሩ በነዚህ አካባቢ ያለው ፍላጎት በሌላ አማራጮች እስኪተካ ድረስ አገልግሎቱ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።
በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባሉባቸው እንዲሁም በውስጥ ለውስጥ ሰፈሮች ዜጎች ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎችን / ባጃጅ ለትራንስፖርት ይጠቀማሉ።
እጅግ በርካታ ዜጎችም በተለይ በተለይ ወጣቶች በዚሁ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ገቢ ያገኛሉ ቤተሰባቸውንም ያስተዳድራሉ።
ከዚህ ቀደም ባጃጆች በተለይ በከተማው ዳርዳር ከዋና ዋና የሚባሉ መንገዶች ወጥተው ውስጥ ለውስጥ ብቻ እንዲሰሩ መደረጉ የሚዘነጋ አይደለም።
#AddisAbaba
#TikvahEthiopia
@tikvahethiopia
❤️
ከአሜሪካ ሃገር በመጡ ሐኪሞች የልብ ሕክምና ተልዕኮ (Mission) አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ የልብ ማዕከል-ኢትዮጵያ ውስጥ " ሃርት አታክ ኢትዮጵያ ' በተሰኘ በአሜሪካን ሃገር በሚገኝ በዶ/ር ተስፋዬ ተሊላ እና ዶ/ር ኦብሲኔት መርዕድ የተመሰረተ የግብረ ሰናይ ድርጅት የነጻ የልብ ሕክምና ተልዕኮ አገልግሎት ከነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ እየሰጠ ነው።
ይህ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀ የሕክምና ተልዕኮ መርሐግብር ነው።
የሕክምና አገልግሎቱ ከማዕከሉ በተጨማሪም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ100 በላይ በልብ ሕመም የሚሰቃዩ ታካሚዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ያቀደ ነው።
የሕክምና አገልግሎቱን ለመስጠት ከ17 በላይ የልብ ሕክምና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የጤና ባለሞያዎች እየተሳተፉ ነው።
ሃርት አታክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኦብሲኔት ፥ " በዚህ ዙር ደረት ሳይከፈት ከሚሰሩ ሕክምናዎች በተጨማሪ የልብ ቀዶ ሕክምና እና የልብ ምት ችግር ላለባቸው ሕሙማን የሚሰጡ ሕክምናዎች ተካተዋል " ብለዋል።
ድርጅቱ ለሕክምና ተልዕኮው ከ1.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን ለሕክምና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን አሰባስቦ ነው ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ነው የጠቆሙት።
ወደፊት ተጨማሪ ተልዕኮዎችን እንደሚያካሂድ አመልክተዋል።
የልብ ማዕከል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኅሩይ ዓሊ ፥ " በዚህ የሕክምና ተልዕኮ ላይ በርካታ ወረፋ በመጠበቅ ላይ የሚገኙ ሕሙማን ተጠቃሚ ናቸው። " ያሉ ሲሆን " ተልዕኮው ስኬታማ እንዲሆን ማዕከሉ ከዝግጅት ጊዜ ጀምሮ አስፈላጊ ሥራዎችን ሲሰራ ነበር ቆይቷል " ነው ያሉት።
#Ethiopia
@tikvahethiopia @thechfe
#Telegram : የቴሌግራም መስራች እና ዋናው ስራ አስኪያጅ ፓቨል ዱሮቭ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
ፍርድ ቤት በ5 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 5.56 ሚሊዮን ዶላር ዋስ ተለቆ ጉዳዩን እንዲከታተል ወስኖለታል።
ከፈረንሳይ እንዳይወጣ ግን ታግዷል።
እገዳው ተጨማሪ ምርመራ ስለሚደረግ ነው የተጣለው።
በሳምንት ሁለት ጊዜ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት ተገልጿል።
ዱሮቭ ከቀናት በፊት ፓሪስ አቅራቢያ ኤርፖት ተይዞ ከታሰረ በኃላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቆይቶ ነበር። ከዚህ በላይ በህጉ ማቆየት ስለማይቻል ከማቆያ ወጥቶ በፍርድ ቤት ጉዳዩ ታይቷል።
ፍርድ ቤቱም ከፈረንሳይ እንዳይወጣ በማገድ የ5 ሚሊዮን ዩሮ ዋስትና ፈቅዶለታል።
የፈረንሳይ መንግስት ዱሮቭ ላይ ምርመራ የከፈተው በቴሌግራም ፦
- ሞደሬት የማድረግ / ቁጥጥር የማድረግ ክፍተት አለ፣
- ለባለስልጣናት አስፈላጊ መረጃ አይሰጥም
- የወንጀል ድርጊቶች ይፈጸምበታል፣
- የአደገኛ እፅ ዝውውር ይከናወንበታል
- ሽብር፣ መኒ ላውንደሪንግ ይሰራበታል በሚል ነው።
ቴሌግራም ወደ 1 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን በነጻነቱና ደህንነቱ በተጠበቀ የመልዕክት እና መረጃ ልውውጥ በብዙዎች ዘንድ እጅግ ተመራጭ ነው።
#TikvahEthiopia
@tikvahethiopia
#ለጥንቃቄ_ከጠቀማችሁ
1. በአዲስ አበባ ከተማ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የምትሰጡ ወንድም እህቶቻችን እባካችሁ ጥንቃቄ አድርጉ።
ማክሰኞ ምሽት 4 ሰዓት ገደማ ወደ ጎተራ ማሰለጫ መውረጃ ወይም በተቃራኒ ወደ ቄራ የሚወስደው መስቀለኛ መንገድ አካባቢ አንድ አገልግሎት ሰጪን 3 ተሳፋሪ መስለው የገቡ ወንበዴዎች መሃል አስፓልት ፣ በብዛት መኪና በሚመላለስበት መንገድ ላይ ከውስጥ እቃ ይዘው ሲሮጡ መመልከቱን አንድ የቤተሰባችን አባል መልዕክት አጋርቶናል።
ሹፌሩ ከመኪና ውስጥ አልወረደም ነበር። ምናልባት ቢወርድ ሌላ የነሱ ተባባሪዎች መኪናውን ይዘው ለመጥፋት አስበውም ሊሆን ይችላል ብሏል።
እነዚህ 3 ሰዎች ሁለቱ ከኋላ አንዱ ከፊት የነበሩ ሲሆን በፍጥነት የመኪናውን በር ከፍተው እቃ ይዘው ሲሮጡ ነው የተመለከታቸው።
" ፈጣሪ ነው የሚጠብቀን ነገር ግን በተለይ ምሽት ላይ ስንሰራ የምንጭናቸውን ሰዎች ፦
- ማንነት፣
- ስልክ ቁጥር ፣
- የምንሄድበትን ቦታ ፣
- የሰዎቹን ሁኔታ ድርጊታቸውን፣
- ንግግራቸውን በደንብ እንከታተል። ውስጣችን ጥሩ ስሜት ካልተሰማውም ይቅርብን " ብሏል።
ህይወታቸውን ለማሻሻል፣ ቤተሰባቸውን ለመደገፍ ፣ ልጆቻቸውን ለማኖር ሲሉ ብርድ እና ፀሀይ እየተፈራረቀባቸው ቀን ፣ ምሽት ፣ ለሊት ሳይሉ የሚሰሩ ወገኖቻችንን ፈጣሪ ከክፉ ይጠብቃቸው።
ዘራፊዎችም ዛሬ ላይ ተይዘው ነገ የሚለቀቁ ከሆነ ከወንብድና ተግባራቸው ስለማይመለሱ እጅግ ጠንካራ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል።
የሰረቁበትን ቀን እንዲረግሙ የሚያደርግ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይገባል።
ሰው ለልጆቹ ፣ ለቤተሰቦቹ ለራሱ ህይወት ሲል ከባድ ዋጋ እየከፈለና በሰላም ጥሩ ሰራተኛ ዜጋ ሆኖ ሀገሩን ህዝቡን እያገለገለ ካለ በበቂ ሁኔታ ከወንጀል ሊጠበቅ ይገባዋል።
2. በመኪና ተደራጅተ የሚዘርፉ ዛራፊዎች አሁንም በከተማው አሉ።
በቅርቡ ፥ መካኒሳ አካባቢ አንድ ግለሰብ በገዛ ሰፈሩ ያውም ጠዋት ላይ በ " ቪትዝ " ተሽከርካሪ የመጡ ወንበዴዎች አንገቱን በማነቅ ንብረቱን ዘርፈው መሬት ላይ ጥለውት ጠፍተዋል።
" አውቶብስ ተራ " አካባቢ በተመሳሳይ አንድ ወጣት በ ' ቪትዝ ' ተሽከርካሪ ላይ በመሆንና ውሃ በመድፋት " ና እንጥረግልህ " በማለት ለመዝረፍ ሙከራ አድርገዋል ፤ ምንም እንኳ ክፉ ሃሳባቸው ባይሳካም።
እነዚህ ባለመኪና ወንበዴዌች ምናልባት ብዙ ቦታ መሰል ተግባራትን እየፈጸሙ ይሆናል።
ከወራት በፊት ሩወንዳ አካባቢ ለሊት በ ' DX መኪና ' ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወንበዴዎች አንድን ግለሰብ ሞባይል ስልክ በገጀራ አስፈራርተው መዝረፋቸውን ነግረናችሁ ነበር።
መኪና የምታከራዩ ወይም መኪና ለሰው የምትሰጡት ሰዎችም ጥንቃቄ አድርጉ ማነው ፣ ለምን አገልግሎት እየተጠቀመ ነው የሚለውን አጣሩ።
ፖሊስ ይህንን ጉዳይ ከምንጩ ለማድረቅ መስራት አለበት።
በከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንገድ ትራፊክ መብራት ላይ ስርቆት በጅጉ ቀንሷል። ይህ አበረታች ተግባር ጭራሽ መኪና ይዘው ለዝርፊያ በተሰማሩ አካላት ላይም መቀጠል አለበት።
ሰዎች ቀንም ይሁን ማታ ሳይሳቀቁ መንቀሳቀስ እንዲችሉ መደረግ አለበት። ህግ ቀን ቀን ብቻ የሚሰራ ማታ የማይሰራ እስኪመስል ድረስ ዘራፊዎች የሚያደርጉን እንቅስቃሴ መገታት መቻል አለበት።
3. የጸጥታ አካላትን የሚመስል ልብስ ለብሰው የሚዘርፉም አሉ።
አንድ የቤተሰባችን አባል በመንገዱ የገመጠውን አጋርቶናል።
ድርጊቱ የተፈጸመው በዚህ ወር አለርት ሆስፒታል አካባቢ ነው።
መኪናውን እያሽከረከረ በሚሄድበት ወቅት የጸጥታ ኃይል ልብስ የሚመስል የለበሱ በግሩፕ የተሰባሰቡ ሰዎች (8-10) ድቅድቅ ያለ ጨለማ ውስጥ ሆነው ሊያስቆሙት ይሞክራሉ።
ነገር ግን እውነተኛ እና ትክክለኛ የጸጥታ አካላት ሰዎች እንዳልሆኑ ይጠረጥራል። ምክንያቱም ከዚህ ቦታ በፊት (ብዙም ሳይርቅ) ሌላ የደህንነት ፍተሻ ተፈትሾ ነበር።
እንዚህ ሰዎች ቁም ያሉት ቦታ ድቅድቅ ጨለማ እና የሚያስፈራ ስለነበር ወደፊት ትቷቸው ሲሄድ ሁለት የተጎዱ ሰዎች መሬት ላይ ተኝተው ተመልክቷል። ሌላ መኪና ስላልነበረና ለህይወቱም በመስጋቱ በፍጥነት ከቦታው ርቆ ሄዷል።
ምናልባት እነዚህ ሰዎች ለፍተሻ ብለው መኪናቸውን አስቁመዋቸው ዘርፈዋቸው ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬውን ገልጿል።
የፖሊስ የደህንነት ፍተሻ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ከየትኛውም አካል ፍቃድ ሳያገኙ ለመሰል እንቅስቃሴ የሚሰማሩ ካሉ አጥንቶ እርምጃ መውሰድ ይገባል። የማያዳግም አስተማሪ ቅጣትም መቀጣት ይገባል።
ሌላው የየትኛውም የሀገሪቱ የጸጥታ ልብስ በሲቪል ሰዎች / አባል ባልሆኑ ሰዎች እየተለበሰ በማኛውም መንገድ ሚዲያ ላይም ጭምር መታየት የለበትም። ሁሉም ሰው ለፍቶ ነው የክብር ልብሱን የሚለብሰውና ማንም እየተነሳ የጸጥታ ልብስ እየለበሰ መታየት ሌላውም ይህን እንዲለማመድ መደረግ የለበትም ፤ ልብሱም መከበር አለበት።
#TikvahEthiopiaFamilyAddisAbaba
#ቲክቫህኢትዮጵያ
#አዲስአበባ
@tikvahethiopia
" የሃሳብ ልዩነቱ ወደ ግጭት አያመራም " - አቶ ጌታቸው ረዳ
ዓመታዊው የ2016 ዓ/ም የአሸንዳ በዓል ዛሬ ነሃሴ 16/2016 ዓ/ም በመላ ትግራይ መከበር ጀምሯል።
በዓሉ እስከ ነሃሴ 24/2016 ዓ.ም አንደሚቀጥል የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
በሌላ በኩል ፕሬዜዳንት ጌታቸው በ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የተገነባ የ10.2 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሲመርቁ ፤ የአሸንዳ አደባባይ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ዳግም የህወሓት ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል የተባሉት ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር ) በተምቤን በመገኘት የቀለም ፋብሪካ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አኑረዋል።
በመቐለ ትንሹ ስታድዮም በተከናወነው ይፋዊ የአሸንዳ ስነ-ሰርዓት ተገኝተው ፥ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉት አቶ ጌታቸው ረዳ " የተፈጠረው የሃሳብ ልዩነት ወደ ግጭት አይሸጋገርም "በማለት ታዳሚውን አረጋግተዋል።
ዓመታዊ የአሸንዳ የሴት ልጃገረዶች በዓል በሽረ-እንዳስላሰ ፣ በአክሱም ፣ በዓድዋ ፣ በዓዲግራት ፣ በተምቤን ፣ በመቐለ ፣ በማይጨውና በሌሎች ከተሞች በድምቀት መከበር ጀምሯል።
#TikvahEthiopia
@tikvahethiopia
#ደመወዝ
" ለግል ድርጅቶች ሠራተኞችም የደመወዝ ማስተካከያ የሚደረግበት አቅጣጫ እንዲሰጥ ለመንግስት ጥያቄ ቀርቧል " - ኢሠማኮ
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት ይፋ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ ለመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ይደረጋል በተባለው ልክ፣ ለግል ድርጅቶች ሠራተኞችም ማስተካከያ የሚደረግበት አቅጣጫ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቧል።
የኢሠማኮ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ፤ " በመንግሥት በጀት ለሚተዳደሩት የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ እንደሚደረግ ቢገለጽም፣ የግል ድርጅቶችና ተቋማት በራሳቸው በጀትና ትርፍ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑናቸው፣ በትርፋቸው ላይ ተመሥርተው ለሠራተኛ የደመወዝ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ከመንግሥት አቅጣጫ እየተጠበቀ ነው " ብለዋል።
" የሠራተኞችና የደመወዝ ዝቅተኛው ወለል እንዲወጣ እየወተወትን ነው " ሲሉም ተናግረዋል።
የመንግሥት እና የግል ሠራተኞች አንዱ የተሻለ አንዱ የወደቀ የሚባል ክፍያ ሊኖር አይገባም ሲሉ አክለዋል።
" መንግሥት ይህን ጉዳይ ሊዘነጋው አይችልም የሚል እምነት ቢኖረንም፣ መሰል አገራዊ አጋጣሚዎችና ቀውሶች በሚኖሩበት ጊዜ ባለሀብቶችንና ተቋማትን የሚመለከቱ ማሻሻያዎች በማድረግና ውይይቶች በማካሄድ አቅጣጫዎች ሊሰጡበት ይገባል " ሲሉ ተናግረዋል።
" ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ለአገርም አይጠቅምም፣ የኢንዱስትሪ ሰላም አይኖርም፣ ሠራተኛውም ተረጋግቶ ሥራውን ማከናወን አይችልም " ብለዋል።
አቶ አያሌው፣ " ጉዳዩ እጅግ በጣም አሳሳቢ ስለሆነ መንግሥት አቅጣጫ የማይሰጥበት ከሆነ ኢሠማኮ ጥያቄውን በጽሑፍ ለመንግሥት ያቀርባል " በማለት አስረድተዋል፡፡
" ሠራተኛው በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ምክንያት በልቶ ማደር አልቻለም፣ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አልቻለም፣ ይህን ማንም ያውቀዋል ሚስጥር አይደለም፣ አሠሪዎቹ ለሚያሠሯቸው ዜጎች ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ መክፈል አለባቸው " ብለዋል፡፡
የሠራተኛ መብት መከበር እንዳለበት " የሚያረጋግጥ ወጥ የሆነ ሕግ ያስፈልጋል " ያሉት አቶ አያሌው፣ " የሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልና ሌሎች የሠራተኞች መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መንግሥት ለምን እንዳዘገያቸው አልገባኝም " ሲሉ ገልጸዋል።
" የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይ ላይ አሁንም መንግሥት የዘነጋው ይመስላል " ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ኢሠማኮ ተጨማሪ ጥያቄ ሊያቀርብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
አክለው ፥ ከመንግሥት ተቋማት በተሻለ የሚያተርፉት የግል ተቋማት፣ ከመንግሥት የደመወዝ ጭማሪ ጋር እኩል ላለመጨመር ትልቁ ችግር የአስተሳሰብ ጉዳይ እንጂ፣ የገንዘብ እጥረት አይደለም በማለት ለዜጎች ማዘን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለራስ ብቻ ከማግበስበስ ዕሳቤ በመውጣት ምርታማ ሠራተኛን ለማፍራት፣ አሁን ተመጣጣኝ የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ብዙ ነው የሚያሰኝ አለመሆኑን ገልጸዋል።
#EthiopianReporter #Salary #Ethiopia
@tikvahethiopia
#Ethiopia
ያለ ውጭ ምንዛሬ ክፍያ (በፍራንኮ ቫሉታ) ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስቴር ለጉምሩክ ኮሚሽንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሰርኩላር አስተላልፏል።
በዚህም ሰርኩላር ፥ መንግሥት በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው የተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬ በገበያው አማካኝነት እንዲወስን ማድረጉ እና ይኸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሷል።
ማሻሻያው የገቢ ንግዱን በይበልጥ እንዲያሳልጥ ወደ አገር እንዳይገቡ በሕግ ክልከላ ከተደረገባቸው ዕቃዎች፣ የነዳጅ አውቶሞቢሎች እና ከፀጥታና ከደህንነት ዕቃዎች ውጪ ሌሎች ዕቃዎች ያለ ውጭ ምንዛሬ ክፍያ (በፍራንኮ ቫሉታ) ወደ አገር እንዲገቡ በመንግሥት የተወሰነ መሆኑና ይኸው ተግባራዊ እንዲደረግ አሳስቧል።
#MinistryofFinance
#TikvahEthiopia
@tikvahethiopia
#አሁን : በመቐለ ከተማ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ በወቅታዊ የህወሓት የፓለቲካ ሁኔት ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ መድረኩ ላይ " 14ኛው የህወሓት ጉባኤ ህጋዊ አይደለም " ብለው የተቃወሙ ፦
➡️ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ፣
➡️ የድርጅቱ የማእከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን ፣
➡️ የክልል ፣ የዞን ፣ የወረዳና ሌሎች አመራሮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
የህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበር ጌታቸው ረዳ፥ " የውይይት መድረኩ ህወሓትን ለማዳንና ትግራይን ወደ ነባራዊ ሁኔታዋ ለመመለስ ወሳኝ ነው " ማለታቸውን ከድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ተጨማሪ ይኖረናል።
የፎቶ ባለቤት ፦ ድምጺ ወያነ
@tikvahethiopia
#Tigray🚨
" የጊዚያዊ አስተዳደሩን ስልጣን ለመንጠቅ የመሞከር እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ብለን እንጠብቃለን " - አቶ ጌታቸው ረዳ
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንትና የህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበር ጌታቸው ረዳ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ዛሬ ነሀሴ 11/2016 ዓ.ም መገለጫ ሰጥተዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች ምንድናቸው ?
- የህወሓትና ሌሎች ህገ-ደንቦች ያላሟለና ተጨባጭ የትግራይ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው።
- የጉባኤው መነሻ የጥቂት የማእከላዊና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ፍላጎት ነው።
- ትግራይ ወደ ከባድ አደጋ እንድትወድቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ከፍተኛ አመራር ተመልሶ ስልጣን ላይ ለመውጣት ያደረገው እንቅስቃሴ ነው።
- ጉባኤው መላው የህወሓት አባላት የሚወክል አይደለም።
- ውጤት እንደሌለው ስለምናውቅ ወደ አላስፈላጊ መሳሳብ ላለመግባት በማሰብ ጉባኤ እንዳያካሂዱ አልከለከልንም።
- ማንነቱ ያልታወቀና ደጀን ይሆነናል የሚሉት ሃይል ተማምነው እያካሄዱት ያለው ጉባኤ ወደ አልተፈለገ ችግር ሊያስገባን የሚችል ነው።
- ድርጊታቸው የመንግስት ስራ መስራት የሚገባቸው አካላት ከስራ ውጪ የሚያደርግ ነው።
- የጊዚያው አስተዳደሩ ስልጣን ለመንጠቅ የመሞከር እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ብለን እንጠብቃለን።
- የትግራይ የፀጥታ ሃይሎች የስልጣን ፈላጊ አካላት መሳሪያ መሆን የለባቸውም።
- ህወሓት መዳን አለባት የምትድነው ግን በያዙት መንገድ አይደለም።
ትላንት የህወሓት ጉባኤ ቃለ-አቀባይ አቶ ኣማኑኤል ኣሰፋ መግለጫ ሰጥተው የነበረ ሲሆን ፤ ጉባኤው እንዲራዘም የሚጠይቅ ጥያቄ በመካሄድ ቢነሳም በጉባኤተኞቹ ወድቅ መደረጉ ተናግረዋል።
ድርጅቱ " አጋጠሞኛል " የሚለው የስትራቴጂክ አመራር ውድቀት ለመፍታት አልሞ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ነው " ቃለ-አቀባዩ ጨምረው ገልፀዋል።
ፎቶ፦ #TigraiTelevision
#TikvahEthiopiaMekelle
@tikvahethiopia
#WachamoUniversity
#በከባድ_የሙስና_ወንጀል የተጠረጠሩት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በአጠቃላይ በ6 ግለሰቦች ላይ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።
የክስ መመስረቻውን የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
ተጠርጣሪዎቹ ፦
1ኛ. የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሀብታሙ አበበ አጊሾ ( ዶ/ር)፣
2ኛ. የዩኒቨርሲቲው አካዳሚና ምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ታምራት ታገሰ ተኮራ (ዶ/ር)፣
3ኛ. ኮንትራክተር የሆነው ደሳለኝ አስረዳ፣
4ኛ. የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ሙላቱ ኤርትሮ ጡንዳዳ፣
5ኛ. የዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ዳይሬክተር ማርቆስ ዮሃንስ ረገዮ እና
6ኛ. የቀድሞ የአዋሽ ባንክ ሆሳህና ቅርጫፍ ስራ አስኪያጅ የነበረው መለሰ ግርማ ኤርጋኖ ናቸው።
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ምን ይላል ?
➡ ተጠርጣሪዎች በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፣ ለንግስት ኢሌኒ መታሰቢያ ሆስፒታል የኦክስጂን ማምረቻ ለማስገንባት መቀመጫውና ዋናው መ/ቤቱን ካናዳ ቶሮንቶ ካደረገ " ኤ. ኤ. ኤምዲ. ቴክኖሎጂ ኢንካ " ለተባለ ድርጅት የመንግስትን የግዢ መመሪያው ባልጠበቀ መንገድ በ5 አመት አፈጻጸሙ እየታየ መከፈል የሚገባውን አሰራሩን በመተላለፍ በውል ላይ የተዘረዘሩ ስራዎች ሙሉ በሙሉ ባልተሰሩበት ሁኔታ ለድርጅቱ የ57 ሚሊየን 383 ሺህ 956 ብር ከ72 ሳንቲም ለታለመለት አላማ ሳይውል በመክፈል ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል።
የውል ማስከበሪያ የውሉን ጠቅላላ ዋጋ 10 ከመቶ ማለትም 117 ሚሊየን 10 ሺህ 859 ብር ከ60 ሳንቲም የውል ማስከበሪያ ሳይቀርብ እና ስራውም በውል ላይ በተገለጸው ጊዜ ሳይጠናቀቅ በመቅረቱ ይህ የውል ማስከበሪያ ዋስትና ቀርቦ ቢሆን ኖሮ ለመንግስት ገቢ መደረግ የነበረበትን ጥቅም አሳጥተዋል።
➡ " ደሳለኝ አስረደ የግንባታ ስራዎች ተቋራጭ " የመምህራን መኖሪያ ቤት ሁለት (2) ህንጻ ግንባታ ስራ ግንቦት 2013 ዓ/ም እና ጥር 2016 ዓ/ም ላይ በተገባው ውል መሰረት ለዚሁ ህንፃ ተቋራጭ በተጋነነ ዋጋ በመስጠት 272 ሚሊየን 170 ሺህ 210 ብር ከ60 ሳንቲም ያለአግባብ ለተጨማሪ የግንባታ ወጪ መደረጉ ፤ ክፍያ በመፈጸም በዚህ ልክ በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስና ለውለታ 26 ሚሊዮን ብር ጥቅም ማስገኘትና ማግኘት።
➡ በዝምድና እንዲሁም በትውውቅ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ባለቤት እህት እና ሌሎች 2 ሰራተኞች ባልሰሩት ስራ በአበል መልክ የዩኒቨርሲቲውን ገንዘብ ያለአግባብ በመመዝበር ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል።
➡ ተጠርጣሪዎቹ ከሌሎች እስካሁን ድረስ እጃቸው ለጊዜው ካልተያዙ ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር በመንግስት ላይ 487 ሚሊየን 333 ሺህ 912 ብር ከ78 ሳንቲም ጉዳት እንዲደርስና ለሌሎች ያልተገባ ጥቅም እንዲያገኙ ተደርጓል።
ዐቃቤ ሕግ 15 ቀን የክስ መመስረቻ እንዲሰጠው ፍርድ ቤትን ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች ዋስታና ጠይቀዋል።
ፍ/ቤት የተጠርጣሪዎችን ዋስትና በማለፍ ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ መፍቀዱን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።
Via https://telegra.ph/FBC-08-15
@tikvahethiopia
#እንድታውቁት
" ከዛሬ ጀምሮ ከአያት አደባባይ ወደ መገናኛ ፤ ከመገናኛ ወደ አያት አደባባይ የተቃራኒ ጉዞ ተከልክሏል " - የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ
በአዲስ አበባ፣ ከአያት አደባባይ ወደ መገናኛ ፤ ከመገናኛ ወደ አያት አደባባይ ድረስ በስራ የመውጫ እና የመግቢያ ሰዓቶች ላይ ይፈጠር የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ በሚል በጊዜያዊ መፍትሄነት ከአያት አደባባይ እስከ ሴንቸሪ ሞል በሁለቱም መስመሮች የተቃራኒ ጉዞ ተፈቅዶ ነበር።
ነገር ግን መጨናነቁን ይፈጥር የነበረው የሳዕሊተ ምህረት አደባባይ በመቀየሩ ከዛሬ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ በሁለቱም መስመሮች የተቃራኒ ጉዞ መከልከሉን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አሳውቋል።
አሽከርካሪዎች ይሄን ተገንዝበው የመደበኛ የጉዞ መስመሮችን ብቻ እንዲጠቀሙ ማሳሰቢያ ተላልፏል።
#AddisAbaba #TMA
#TikvahEthiopia
@TikvahEthiopia
#Update #GambellaUniversity
“ አዲስ ዳይሬክተር ተመድቦ ' ይነሳልን ' ያሉት ሰው #ተነስቷል ” - የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ዩኒቨርሲቲው ሪፎርም ቢያደርግም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻው የፋይናንስ ጉዳይ እንዳልተደረገ፣ በዚህም ችግሩ በተለይ ከክፍያና ከስልጠና ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፒቲሽን አሰባስበው ዩኒቨርሲቲውን ቢጠይቁም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልጸው፤ “ በቢብስብን ነው ወደ ህዝብና ፊትና ሚዲያ የመጣነው ” ብለው የነበረ ሲሆን፤ ቲክቫህ ኢትዮጵያም ለቅሬታው ምላሽ ተሰጥቶ እንደሆነ ዩኒቨርሲቲውን ጠይቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ደሪባ ኢቲቻ (ዶ/ር) ምን ማላሽ ሰጡ ?
“ ከዚህ በፊትም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ቅሬታውን አቅርበው ቅሬታውን አክኖሌጅ አድርገን በአሰራር ለውጥ ለማምጣት ከተወሰኑ መምህራን ጋር ውይይት አድርገናል፡፡
እንደተባለው በዩኒቨርደሲቲ ደረጃ ሪፎርም ተደርጓል፡፡ ያ ማለት ከዚህ በፊት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ካለው አፈጻጸም አንጻር መዘጋት አለበት ተብሎ፤ ከሚዘጋ ደግሞ ሪሮርም መደረግ አለበት ተብሎ ከፍተኛ የአመራር ለውጥ ተደርጓል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል አለበት የሚል እምነት አለን እኛም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ያለተማሪዎችና ያለመምህራን የሚሰራው ሥራ የለም፡፡
ስለዚህ መምህራን የጠየቋቸውን ጥያቄዎች ላለመመለስ ሳይሆን ወደ ሚዲያም የወጡበት 'በ72 ሰዓታት ውስጥ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እርምጃ ካልተወሰደ ከዩኒቨርሲቲ በላይ ላሉት አካላት ሪፖርት እናደርጋለን ' ብለው ነው፡፡ ያንን ደግሞ እኛ መከልክል አንችልም፡፡
ፋይናንስ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች አገልግሎት አሰጣጣቸውን በዬጊዜው እንዲያሻሽሉ አድርገናል፡፡
ሪፎርም አልተደረገም ማለት አልችልም ምክንያቱም እኛ ሥራ ስንጀምር የነበረውን ዳይሬክተር (ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ክፍተት አለበት የተባለውን ሰው) አንስተናል ከዛም በፊት፡፡
አሁን እዛው ክፍል የነበረ በቡድን ደረጃ ያለውን በጊዜያዊነት ነው ያስቀመጥነው፡፡ እሱንም ደግሞ ለማንሳት መጀመሪያም ፒቲሽን አቅርበው ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ፒቲሽን በሚያቀርቡበት ጊዜ ያለውን አብረን ተነጋግረናል እንደምናስተካክል፡፡
ትልቁ ችግር በቂ ፋይናንስ ባለመኖሩ ሁሉንም ጥያቄ በአንዴ መመለስ አይቻልም፡፡ ብዙ ሪፎርም ያደረግንባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ 'በ72 ሰዓታት ውስጥ' የሚባለው ግን ፋይናንስ ላይ የሚሰራ ሰው ሰነድ ማስረከብ አለበት፡፡ የኮሚዩኒኬሽን ክፍተት ነበረ ይህንን ሲያስተባብሩ ከነበሩ መምህራንና በከፍተኛ ማኔጅመንት።
የ10 ዓመት እድሜ ታሪክ ያለው ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ እንዳሉትም ላብራቶሪ በትክክል ሰርቪስ አልተደረገም፡፡ ግን መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት እየተሰራ ነው ያለው አሁን፡፡ ለመምህራን እውነት ለመናገር ትልቅ አክብተሮት አለን፡፡
የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጣቸው ስለሚፈልጉ፣ ስለጓጉ ነው እንጂ፡፡ ይህም መብታቸው ነው፡፡ ለምን ይህንን አደረጉ አንልም፡፡ ግን መሻሻል እንዳለበት ከእነርሱ ጋርም ተነጋገረናል፡፡ ግልጽ ነው፡፡ እነርሱ ፒቲሽን አመጡም አላመጡም ያው ሪፎርሙ ይቀጥላል፡፡
ችግሩ ወዲያው የማይቀረፈው በኢትዮጵያ ደረጃ አዲስ የሠራተኛ ምደባ ተደርጓል፡፡ አዲስ ቅጥር ደግሞ በሲቪል ሰርቪስ አይፈቀድም፡፡ ቅጥር ተፈቅዶ ገና በፕሮሲጀር የሚከድበት ነው፡፡ የሰለጠነ ባለሙያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማግኘት ይከብዳል፡፡ ጠይቀናል፤ ሊሳካ አልቻለም፡፡
' በ72 ሰዓት ምላሽ ስጡን ' የሚለውም ቢያልፍ እኛ ወስነን ስለነበረ አዲስ ዳይሬክተር ተመድቦ ይነሳልን ያሉት ሰው ከዛ ተነስቷል፡፡ ባይሉም እኛ እንደ ከፍተኛ አመራር ይህንን ወስነናል፡፡ መወሰናችንን ደግሞ አስቀድመን ነግረናቸዋል፡፡ አሁን ያለው እውነታ ይሄ ነው፡፡
በቂ በጀት የለም፡፡ ፍላጎትና በጀት ስለማይመጣጠን ቅድሚያ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ የ2015 ዓ/ም ያልተከፈሉ እዳዎች እንደተባለው የ12ኛ፤ የዊኬንድ፤ የኦቨርሎድ ክፍዎች እየተከባለሉ መጥተው 2016 ዓ/ም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡
ለመምህራን ስልጠና አለመስጠት፣ ወርክሾፕ ላይ ላብራቶሪ አለማሟላት የተፈጠረው የበጀት እጥረት በመኖሩ ነው፡፡ እጥረቱ ደግሞ እንዲፈታ ከፌደራል ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተበነጋርን ነው፡፡
በጀትና የምናቅፀደው እቅድ አለመጣጣም ነው፡፡ አንዱ ያነሱት ቅሬታ 'እዛ ያለው ኃላፊ ይነሳልን' የሚል ነው ተነስቶላቸዋል፡፡ ይህንንም ኮሚዩኒኬት አድርገናል፡፡ መምህራንም አሁን ሥራዎችን እየሰሩ ነው፡፡ እንደተባለው ግን በ72 ሰዓት የተባለውን አንደርስታንድ መደራረግ ያስፈልግ ነበር፡፡
ይህንን ፒቲሽን ከተፈራረሙ በኋላ መምህራንን ለማነጋር እየሄድንብት ያለውን ፕሮሲጀር ለማስረዳት ቀጠሮ ይዘንላቸው እኔ ሌላ ስብሰባ ነበረኝ፤ የአስተዳደርና የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲያገኟቸው ወደ አዳራሽ ሲሄዱ አንድም ሰው እዛ አልተገኘም፡፡
ነገር ግን አሁን አዲሱ ሪፎርም ላይ ባለው አመራር 24 ሰዓት በራችን ክፍት ነው፡፡
ከእነርሱ የምንደብቀው ነገር የለም አንድ ላይ ነው የምንሰራው፡፡ ቀጠሮም ይዘንላቸው እዛ ላይ አልተገኙም ” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ክፍተት እንደነበረበት መረጃዎች መውጣታቸው ይታወሳል፤ ለመሆኑ እርምጃ ተወስዷል ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላቀረበው ጥያቄ፤ የማስተካከያ እርምጃዎች እንደተወሰዱ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
“ ኮመንት የተደረጉት የፌደራሉ ኦዲት መስሪያ ቤት የአመቱን የኦዲት ሪፖርት ይጠይቃል፡፡ ግኝቶቹ ላይ በቂ ማብራሪያ ወይንም ግብረ መልስ ተሰጥቷል ” ነው ያሉት፡፡
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#Infinix_Note40_Pro_Plus
ኢንፊኒክስ አዲሱን የኖት 40 ፕሮ ፕላስ 5G ስልኩን እጅግ ደማቅ በሆነ የጌሚኒንግ እና የሙዘቃ ዝግጅት በቃና ስቱዲዮ ለተጠቃሚዎች አስተዋውቋል!
በተለይም ለጌመሮች እና ለሙዚቃ አድናቂዎች የተለየ ነገርን ይዞ የመጣው አዲሱ የኢንፊኒክስ ኖት 40 ፕሮ ፕላስ 5G ስልክ ነሀሴ 4 በቃና ስቱዲዮ በአይነቱ ለየት ባለ ዘግጅት አዲሱን ስልኩን አንዲሁም የኢንፊኒክስ ቲቪ፣ ላፕ ቶፕ ፣ ስፒከሮች፣ ስማርት ዋች እና ኤር ፖዶችን ለተጠቃሚዎች አስተዋውቋል፡፡ አዲሱ የኢንፊኒክስ ኖት 40 ፕሮ ፕላስ 5G ስልክ 108 ሜጋ ፒክስል ጥራት ያለው የካሜራ ቴክኖሎጂ ይዞ የመጣ ሲሆን 100 ዋት ፋስት ቻርጀር እና 20 ዋት ያለገመድ ዋየር ለስ ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ በተጨማሪም የዘመኑ የመጨረሻ የኔትወርክ ቴክኖሊጂ የሆነውን 5G ኔትወርክን ማስጠቀም የሚያስችል አቅም ያለው ሲሆን በጌመሮች እና ከፍተኛ አቅም የሚፈልጉ ስራዎችን በስልካቸው በሚከውኑ ስዎች ተመራጭ የሆነውን የ Mediatek Dimesnty 7020 ፕሮሰሰርን የተገጠመለት ፈጣን ስልክ ነው፡፡
#Note40Et #Note40Pro #Note40 #Note40ProPlus #InfinixEt
#FederalGovernment #TPLF
" አላስፈላጊ እና ሕዝብን የማይጠቅም፣ ትርጉም አልባ ንትርክን አስወግደን ለሕዝብ ረብ ያላቸው ጉልህ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ልናተኩር ይገባል " - የፌዴራል መንግሥት ኮሚኒኬሽን
የፌዴራል መንግሥት ኮሚኒኬሽን በህወሓት ጉዳይ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል።
በዚህ መግለጫ ፦
- ህወሓት እንዴት ሕጋዊ ሰውነቱን ሊያጣ እንደቻለ ወደኃላ መለስብሎ አስታውሷል ፤
- የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈጸም የፌዴራል መንግሥት በስምምነቱ የገባው ግዴታ የህወሓት የሽብርተኝነት ፍረጃ እንዲነሣ ሂደቱን የማሣለጥ ኃላፊነት (የስምምነቱ አንቀጽ 7 (2) (C)) እንደሆነ ፤
- የፌዴራል መንግሥት የህወሓትን የሕግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ እንዳልነበር፤
- ህወሓት በፕሪቶሪያ ስምምነት እንቀጽ 7 (1) (A) መሠረት የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት፣ ሕጎች፣ የፌዴራል ተቋማትን እና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ሥልጣን የማክበር ግዴታ መግባቱም ፤ ስለዚህ ሕወሐት የሀገሪቱን የፖለቲካ ፖርቲዎች የምዝገባ ሕግ እና የምርጫ ቦርድን ሥልጣን በማክበር የመሥራት ግዴታ እንዳለበት ... ገልጿል።
የፌዴራል መንግሥት በመግለጫው ፤ ህወሓት ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት ስለተኬደባቸው መንገዶች ፣ ውይይቶች ፤ በህወሓት እና ምርጫ ቦርድ በኩል ስለተነሱት ልዩነቶች አብራርቷል።
ድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነት እና ዕውቅና እንዲኖረው ለቦርዱ የትብብር ጥያቄ ስለማቅረቡም አስታውሷል።
እንዲሁም አዋጅ እስከማሻሻል በደረሰ እርምጃ ድርጅቱ ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገባ ለማድረግ የተኬደበትን ርቀት ገልጿል።
ይህን ተከትሎ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እና ዕውቅና ለማግኘት የሚጠበቅበት የፓርቲ ሰነዶቹን ማለትም የፓርቲውን ፕሮግራም እና ሕገ ደንብ፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሰነዶችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማቅረብ በተሻሻለው አዋጅ መሠረት ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት እንዳገኘ አሳውቋል።
በመሆኑም " የምዝገባ እና የህግ ሰውነትን ጉዳይ በዚህ በመቋጨት፤ የሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ ሰላምን በማጽናት፣ በመልሶ ግንባታ እና በልማት አጀንዳ ላይ ሊሆን ይገባል " ብሏል።
ፌዴራል መንግሥት" አላስፈላጊ እና ሕዝብን የማይጠቅም፣ ትርጉም አልባ ንትርክን አስወግደን ለሕዝብ ረብ ያላቸው ጉልህ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ልናተኩር ይገባል " ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)
@tikvahethiopia
#Ethiopia
አትሌቲክሳችን ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል። ይህ መሆን ያለበት ደግሞ በትክክለኛ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ነው።
የኦሎምፒክ ውጤቱ አንገት የሚያስደፋ ነው።
በጭቅጭቅ፣ በንትርክ፣ በየሚዲያ ላይ በሚደረግ ምልልስ የተጀመረው የፓሪስ ውድድር ኢትዮጵያን የማይመጥን እጅግ ዝቅ ያለ ውጤት ተመዝግቦበት አልቋል።
ጥፋት ከደረሰ እና ውጤት ከጠፋ በኃላ የሚቀርብ ይቅርታ ተቀባይነት የለውም።
የሚያስፈልገው ሁሉም የአትሌቲክሱ ቤተሰብ ቁጭ ብሎ በእርጋታ መክሮ ፤ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ብቻ ነው።
ሁሉም ዜጋ በየፊናው የተሰማውን ብስጭት፣ ንዴት እየገለጸ ነው። ይህ የሚጠበቅ ነው። ምክንያት ? ሀገሩ ነው፣ ክብሩ ነው። የሚጠብቀውን ሳያገኝ ሲቀር ህዝቡ ያዝናል ፣ይበሳጫል።
እውነትም " ለሀገራችን ክብርና ፍቅር አለን " የሚሉ የአትሌቲክሱ አካላት በእርጋታ ፣ በንግግር ችግሮች እንዲፈቱ ያድርጉ።
ይህም በመሪዎች እና አመራሮች ደረጃ " ለጠፋው ውጤት ፣ ዝቅ ላለው የህዝባችን ክብር ኃላፊነት እንወስዳለን ፤ ይህ የመጣው ስላልሰራን ነው " ብሎ ቦታ መልቀቅን ፤ ለሌላው እድል መስጠትን ያካትታል።
በአትሌቶች ዘንድም የውጤታችን መጥፋት እንዴት እንደተከሰተ ፤ ምናልባት የተሻሉ አትሌቶችም ካሉ ለነሱ ቦታ እያስረከቡ መሄድም እንዲቻል በጥልቀት መገምገም ይገባል።
በአትሌቶች እና አሰልጣኞች መካከልም ተግባብቶ እንደ አንድ ሀገር ዜጋ በቡድን አለመስራት ችግርም ካለ መፈተሽ አለበት።
ከምንም በላይ ግን ዘርፉን የሚመሩትን አካላት እና እዛ አካባቢ ያሉትን በሙሉ በጥልቀት መገምገም ይገባል።
በአጠቃላይ ስር ነቀል ለውጥ መምጣት አለበት።
ህዝቡ የሚፈልገው ክብሩ እንዲመለስለት ብቻ ነው ፤ ሙያውን የሚያውቅ በቦታው ተገኝቶ ለውጥ አምጥቶ በሀገሩ ውጤት ተደስቶ ማየት ነው።
የሚዲያ ምልልስ ፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ በዚህ መሃል ደግሞ የሚፈጠር የውጤት ውድቀት ህዝብን ፍጹም አይመጥንም።
ጉዳዩ ሙያዊነውና ለባለሙያዎቹ እንተወው ፤ እውነት ግን " የሀገራችን ክብር ይመለከተናል " የሚሉ የሀገር ጉዳይ ብቻ አላማቸው ከሆነ ሌላ ፍላጎት ከሌላቸው ጭቅጭቅ እና ንትርክ ትተው ቁጭ ብለው መነጋገር አለባቸው። ኃላፊነት መውሰድም አለባቸው።
በአሁኑ ውጤት ያልተበሳጨ፣ ያላዘነ ፣ አንጀቱ ያላረረ ዜጋ የለም በዚህም ደግሞ በስሜታዊነት አስተያየቱን እየሰጠ ነው። ለውጥ እንዲመጣ ወደ ክብራችን እንድንመለስ ጥያቄ እያቀረበ ነው።
ነገር ግን አንዳንድ አስተያየቶችም ጥንቃቄ ይፈልጋሉ የአትሌቶችን ስነልቦና እንዳይጎዳ።
ባለፈው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና " ያለእናተ ሰው የለም ፤ ጀግኖች " እያልን ያወደስናቸውን ልጆች ዛሬ ውጤት በመጥፋቱ በብስጭት እና ሀዘን ስሜት ያልተገባ ቃል እንዳንናገር መጠንቀቅ ይገባል።
ዳግም ህዝቡ በሚኮራበት #አትሌቲክስ እንዳያዝን እና እንዳይበሳጭ ተነጋግሮ ስር ነቀል ለውጥ መምጣት አለበት።
ህዝቡ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ክብሩ እንዲመለስለት ይፈልጋል፤ አራት ነጥብ !
ስር ነቀል ለውጥ ለኢትዮጵያ 🇪🇹 አትሌቲክስ !
#የሐሳብ_መድረክ @nousethiopia
@tikvahethiopia
#ዕለታዊ_ምንዛሬ
የዶላር ዋጋ ባለፉት ተከታታይ ቀናት ከነበረው ዛሬ ጭማሪ አሳይቷል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 7 ቀናት ጭማሪ ሳይታይ ወጥ ሊባል የሚችል የምንዛሬ ዋጋ ነበር።
በዛሬው ዕለት ዶላር መግዣው ወደ 105.4304 ከፍ ሲል መሸጫው ወደ 117.0277 ጨምሯል።
ፓውንድ መግዣው 132.5631 ፤ መሸጫው 147.8322 ገብቷል።
ዩሮ 116.7747 መግዣው ሲሆን 129.6199 መሸጫው ነው።
በግል ባንኮች አንዱ ዶላር መግዣው ከ104 ብር አንስቶ እስከ 120 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው።
(በተለያዩ የግል ባንኮች ያለው የምንዛሬ ዋጋ ከላይ ተያይዟል)
@tikvahethiopia
#Urgent🚨
በአማራ ክልል፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ፣ ጠለምት ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የበርካታ ወገኖቻችን ህይወት አልፏል።
በርካቶችም ችግር ላይ ወድቀዋል፤ ተፈናቅለዋል።
ለተፈናቃዮቹ አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋል።
ደጋግ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ወረዳው በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ጥሪ አቅርቧል።
የወረዳው አስተዳደሪ አቶ ጋሻው እንግዳው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡት ቃል ፦
“ አካባቢው ከዚህ ቀደም በድርቅ የተጠቃ ነው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለተፈናቀሉት ነዋሪዎች ደግሞ ከ14, 400 በላይ እህል ያስፈልገናል።
የእርዳታ ምግብ ድጋፍ ፤ 480 ድንኳን / ሸራ ፣ እንደ ብረት ድስት፣ ሳፋ አይነት የቤት ቁሳቁሶች በአስቸኳይ የሚያስፈልጉ ናቸው። ”
#TikvahEthiopiaFamyAA
@tikvahethiopia
#GERD🇪🇹
ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ የላብና ደም አሻራ ያረፈበት የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ የአይን ብሌኑም ጭምር ነው።
ተማሪው ፣ ሰራተኛው ፣ ወጣቱ ፣ አዛውንቱ ለዚህ ግድብ ካለው ላይ ፤ ከሚበለው ቀንሶ ሰጥቶ ያሰራው ለትውልድ የሚያወርሰው ሀብቱና ቅርሱ ነው።
ይህ ግድብ ሀገር ውስጥ በየጊዜው በሚፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ሀዘን፣ መከፋት፣ መበደል ሲመጣ እንኳን ሁሉም የውስጡን በውስጡ ይዞ " ሀገሬ ትቅደም " ብሎ ተጠናቆ በአይኑ ለማየት ሲል ብዙ ዋጋ የከፈለለት ነው።
በፖለቲካ አቋም፣ በሃሳብ፣ በአመለካከት እየተለያየ እንኳ የሀገሩን ጥቅምና ግንድቡን የሚነካበት ነገር ሲመጣ ሁሉን ጥሎ ሽንጡን ገትሮ የተራከረለት ፣ እስከመጨረሻው ድረስም ዋጋ የሚከፍልለት ነው።
ይህ ግድብ ገና ከመሰረቱ እንዳይገነባ ፤ ድጋፍም እንዳይመጣ ሲሯሯጡ የነበሩ ብዙ ናቸው።
እንዳይሳካ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ፤ ያልሄዱበት ቦታ የለም። ግን አልሆነም ፤ ወደፊትም አይሆንም።
ዛሬም እነዚህ አካላት ለኢትዮጵያ እንደማይተኙ ግን ግልጽ ነው።
ኢትዮጵያ " የሰው ድርሻ አንድም አልነካም፤ የራሴን ግን እጠቀማለሁ " ማለቷ የሚያንጨረጭራቸው ሀገራት በግንባታው ወቅት ዛቻ ሲያዘንቡ ፣ እንዲቆም ለማስፈራራት ሲሞክሩ ፣ በአንድም በሌላ በዓለም አቀፍ መድረክ በውስጥ እና በይፋ ጫና ለማድረግ ሲሰሩ እንደከረሙ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ብዙ ብዙ ቢሞክሩም መክነው ቀርተዋል። አሁንም ግን ጩኸታቸው እንደቀጠለ ነው።
ለማደናቀፍ የሚደረገው ጥረትም እንደዛው እንደቀጠለ ነው።
አንዴ " የመሬት መንቀጥቀጥ ቢመጣ አይፈርሳል " ፤ አንዴ " ጥራቱ አስተማማኝ አይደለም ይደረመሳል " ፤ አልሆን ሲላቸው " በአየር እንመታዋለን ፣በቦንብ እናጋየዋለን " በማለት ብዙ ሲያወሩ ከርመዋል።
ከወሬ የዘለል ግን ምንም ማድረግ አይችሉም።
እዛው ያሉበት ሆነው የፈለጉትን ማሰብ ይችላሉ ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እያለ ግን ማድረግ መንካት ግን ፈጽሞ አይቻልም።
#Ethiopia
#GERD
#TikvahEthiopia
#ቲክቫህኢትዮጵያ
@tikvahethiopia
#ጉምሩክ
🔴 “ በኢንቮይስም ከፍለን እቃው በገባበት ቀን ነው የምንሰራላችሁ አሉን ” - አስመጪዎች
⚫️ “ በሁሉም ጉዳይ አቤቱታ ይቀርባል አቤቱታ የቀረበበት ሁሉ ተቀባይነት የሚያገኝበት ሁኔታ አይኖርም” - ኮሚሽኑ
ጉምሩክ ኮሚሽን ከማክሮ ኢኮኖሚ ፓሊሲ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ባወጣው አዲስ መመሪያ "ከእጥፍ በላይቀረጥ ክፈሉ'' እየተባሉ መሆኑን አስመጪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ኮሚሽኑም ከቅሬታው በኋላ ማሻሻያ ማድረጉን መረጃ ነግረናችሁ ነበር።
ሆኖም ከ150 በላይ የሚሆኑ “ በኢነቮይስ ከፍለናል ” የሚሉ አስመጪዎች፣ ኮሚሽኑ ከማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራወሰ በኋላ ያወረደውና በአስመጪዎች በኩል “ አዋጅን በደብዳቤ ሽሯል ” በሚል ቅሬታ ቀርቦበት ኮሚሽኑ በድጋሚ ማሻሻያ አደረኩበት ያለው ደብዳቤም ቅሬታቸውን እንዳልፈታላቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
በዚህም እንዲያወያያቸው ጭምር ኮሚሽኑን በደብዳቤ እንደጠቁ ሆኖም ምላሽ እንዳልጠሰጣቸው ገልጸው፤ ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤነው በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል አሳስበዋል።
አስመጪዎች በዝርዝር ያቀረቡት ቅሬታ ምንድን ነው ?
“ ደብዳቤው (ማስተካከያ የተደረገበት) መልስ ስላልሰጠን መልሰን ደብዳቤ ፃፍንላቸው፡፡ ምክንያቱም ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በፊት የገቡ እቃዎች እንዲስተካከሉ ተብሎ ብዙዎቹም አውጥተዋል፡፡
የእኛ ጥያቄ፤ ቅድሚያ እቃው ዶኩሜንት እንደደረሰን ጂቡቲ ላይ እንዳለ በኢንቮይስ ዲክላራሲዮን ይቆረጣል። ጂቡቲ ጭነት ሊዘገይ ስለሚችል ፤ በየሳምንቱ ደግሞ ሬት ስለሚቀይር ያንን ነገር እንዳይነካው ሁሉም ነጋዴ ከዚህ በፊት ለዓመታት የሰራው በዚህ አይነት አካሄድ ነው፡፡
እቃው ጂቡቲ እያለ ዶኩሜንቱ ከመጣ በኢንቮይስ ይከፈላል። ቀሪ ሂሳብ ደግሞ ከፍተሻ በኋላ 'ይለቀቅ' ሲባል ያኔ ተከፍሎ ይመጣል፡፡ አሁን ግን በኢንቮይስም ከፍለን 'እቃው በገባበት ቀን ነው የምንሰራላችሁ' አሉን፡፡
እኛ ደግሞ አልተስማማንም፡፡ ጉምሩክ በገባበት ሳይሆን ዶኩሜንት ባስገባንበት፤ ዲክራላሲዮን ባስቆረጥንበት ነው መስተናገድ ያለብን፡፡ 5 ሚሊዮን ስንከፍል የነበርነው 10 ሚሊዮን፣ 10 ሚሊዮን ይከፍል የነበረ 20 ሚሊዮን ብር ከፈሉ እየተባልን ነው፡፡
አሁን ጠዋት አንድ ሬት ከሰዓት ሌላ ሬት አለው ጉምሩክ፤ ድሮ ግን በየሳምንቱ አንድ ሬት ነበረው፡፡ ሐሙስ ቀን የሚቀየር ሬት ብቻ ነበር የሚሰጡት፡፡
ይህ ደግሞ ኪሳራና ተጠቃሚውም ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚጣመጣበት ጉምሩክም ይገነዘባል፡፡ ይህን ነገር ቢያስተካካል ባለው ዋጋ መሸጥ ይቻላል ” ነው ያሉት፡፡
ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ለቀረበው ቅሬታ የኮሚሽኑ ምላሽ ምንድን ነው ? ኮሚሽኑ ባለፈው አደረኩት ባለው ማሻሻያ የአሁኖቹ ቅሬታ አቅራቢዎችን ጉዳይ አካቶ ምላሽ ሰጥቷል? ከሆነ እንዴት ? ሲል ጉምሩክ ኮሚሽኑንን ጠይቋል።
የኮሚሽን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን አሰፋ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
“ ኮሚሽኑ የተለዬ ምላሽ የለውም ከዚያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ። የተሰጠው ምላሽ ሁሉንም ጉዳዮች ከቨር ያደረገ ስለሆነ ቀደም ሲል በወጣ ደብዳቤ ምላሽ የተሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡
የተለዬ ኮሚሽኑ የሚያየው ጉዳይ የሌለ መሆኑን ነው የማውቀው። ሁሉም ጉዳዮች እዛ ላይ ቴኪኒካሊ ከጉምሩክ አዋጅ አንጻር ታይተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
አጠቃላይ ነው ባለፈውም አቤቱታ የቀረበው፡፡ ስለዚህ ምላሽ የተሰጠበት አግባብ አለ፡፡ በሁሉም ጉዳይ አቤቱታ ይቀርባል አቤቱታ የቀረበበት ሁሉ ተቀባይነት የሚያገኝበት ሁኔታ አይኖርም፤ ይታወቃል።
'መስተናገድ የለብን በዚህ የሚል ጉዳይ' ካለ ኮሚሽኑ የሰጠውን ምላሽ መቃወም መብት ነው። ተራ ቁጥር 1፣ 2፣ 3፣ 4 በሚሉ ተራ ቁጥሮች ላይ ተገልጿል፡፡
የተቀመጡት ኮንዲሽኖች ጂቡቲ ላሉት እቃዎች፣ አገር ውስጥ ላልገባ እቃ በነባሩ የውጭ ምንዛሪ እንስተናገድ ነው ጥያቄያቸው። ያነም ኮሚሽኑ ደብዳቤው ላይ በገለጸው ልክ (ተራቁጥር አራት ይመስለኛል) በግለጽ የተቀመጠ ጉዳይ ነው።
እነርሱ አቤቱታቸውን መቀጠል ይችላሉ፤ ኮሚሽኑ እኮ ከዚህ አንጻር የከለከለው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ የተሰተው ምላሽ ይሄው ነው ከዚያ ውጪ የተለየ የሚሰጥ ምላሽ የለንም በዚያ ደብዳቤ ተመልሶ ያለፈ ጉዳይ ስለሆነ” ብለዋል።
#TikvahethiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
" ከተያዘው እቅድ ውጭ እኛ የማናቀውን ስብሰባ ማካሄድ አይቻልም " - የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር
በትግራይ ክልል ፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ጊዚያዊ አስተዳደሩ የማያውቀው ማንኛውም ሰብሰባ ማካሄድ የሚከልክል የስራ መመሪያ ይፋ ተደረገ።
ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፅህፈት ቤት በፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ ፊርማ ለሁሉም
- የዞን አስተዳደሮች
- ለወረዳ አስተዳደሮች
- የክፍለ ከተማ አስተዳደሮችና
- የወረዳ ምክር ቤቶች
የተላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ጊዚያዊ አስተዳደሩ ከፈቀደው ውጪ ሌላ ስብሰባ ማካሄድ አይቻልም ይላል።
➡️ የኮሌራ በሽታ መከላከል
➡️ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው መመለስና የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ማስከበር
➡️ የ2016 ዓ.ም በጀት መዝጋትና የ2017 ዓ.ም በጀት ማዘጋጀት ... ሌሎች ህዝባዊና መንግስታዊ እቅዶች የጊዚያዊ አስተዳደሩ መሆናቸው የጠቀሰው የስራ መመሪያው ፤ " ከዚህ ውጪ የሚደረጉ ሰብሰባዎች የተያዘው እቅድ ስለሚጎዱ አይፈቀዱም " ብሏል።
ከላይ ከተጠቀሱት እቅዶች ውጪ ማሰተናገድ የጊዚያዊ አስተዳደሩን ስራ በማደናቀፍ #ተጠያቂነት_የሚያስከተል መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቋል።
የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ይህኑን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል።
#TikvahEthiopiaMekelle
@tikvahethiopia
🔈 #የአርሶአደሮችድምጽ
ሲዳማ !
" የማዳበሪያ ችግር የለም ተብሎ በሚዲያ ቢነገርም በቂ ማዳበሪያ እየደረሰን አይደለም " - የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች
ከሰሞኑ " ዘር ካልገዛችሁ ማዳበሪያ አይሰጣችሁም ተባልን " ያሉ የሀዋሳ ዙሪያ አርሶ አደሮች ቅሬታ ማቅረባቸዉን ዘግበን ነበር።
በወቅቱ የማዳበሪያ ችግር እንደሌለና ወደግብርና ቢሮ በመምጣት መዉሰድ እንደሚቻል ከምርጥ ዘር ጋር በተያያዘ አርሶአደሩን የሚጠቅም አካሄድ መሆኑን ይሁንና ገበሬዉ የራሱ ዘር ካለዉ እንደማይገደደ ተገልጾም ነበር።
ይሁንና ከመረጃዉ በኋላ " የማዳበሪያ ችግር የለም " ተብሎ በሚዲያ ምላሽ ከመሰጠቱ በላይ በስብሰባ ወቅት " መጋዝናችን ሙሉ ነዉ " ብንባልም በአግባቡ እየተሰጠን አይደለም ሲሉ በድጋሜ የአካባቢዉ አርሶአደሮች ቅሬታ አቅርበዉልናል።
" አሁን ላይ የዘር ወቅት እያለፈ በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት ዉስጥ ገብተናል " የሚሉት አርሶ አደሮቹ " አራትና አምስት ኩንታል ለሚያስፈልገዉ አምስት ሄክታር የለሰለሰ ማሳ አንድ ኩንታል ብቻ ስለምን እንደሚሰጠን አይገባንም " በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
" ማዳበሪያዉ በቂ አለመሆኑን የአካባቢዉ የግብርና ባለሙያዎች ያውቃሉ። እንደኛ ከማዘን ዉጭ መፍትሄ መስጠት አልቻሉም " ሲሉ ገልጸዉ ጉዳዩ በአመራሩ እጅ መያዙን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፥ " ቀኑን ሙሉ ስራ በመፍታት መጋዝን በር ላይ የሚዉለዉ አርሶ አደር ሀያ ሰላሳ ሰዎች ከተስተናገዱ በኋላ ወደቤታችሁ ሂዱ ይባላል በማለት መጋዝኑን የሞላዉ ማዳበሪያ ለማን ነዉ ? " በማለት ጠይቀዋል።
ከሳምንት በፊት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ " የማዳበሪያ ችግር የለም ከአካባቢዉ አርሶ አደር ጋርም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል " ያሉት የወረዳዉ አስተዳዳሪ " መሬቱን ያዘጋጀ ገበሬ የፈለገዉን ያክል ማዳበሪያ መዉስድ ይችላል " በማለት አንዳች ቅሬታ ያለበት አርሶ አደር ካለ ሊያናግረን ይችላል ማለታቸዉ ይታወሳል።
#TikvahEthiopiaFamilyHW
@tikvahethiopia
ትግራይን ዳግም ወደ ጦርነት የሚያስገባ ተጨባጭ ስጋት አለ ?
" ይሄ የአንድ ድርጅት ጉዳይ ነው። ወደ ጦርነት የሚያስገባ ምንም ነገር የለም " - አቶ አማኑኤል አሰፋ
በሊቀ - መንበሩ ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የ14ኛው የህወሓት ጉባኤ ቃል አቀባይ አማኑኤል አሰፋ ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ነገር የለም ብለዋል።
አቶ አማኑኤል ፥ " በአንድ አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ተሰብስቦ ስለ አንድ ድርጅት ውስጣዊ ጉዳዮች መወሰን ወደ ጦርነት የሚያስገባ አንድም ምክንያት የለም " ሲሉ ተናግረዋል።
" ጦርነት በዚህን ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ ርካሽ አይደለም " ብለዋል።
" ጦርነት አስፈላጊ ሆኖ አማራጭ ቢሆን ኖሮ ትግራይ ውስጥ ያሉት ችግሮች ሌላ ጦርነት ይጋብዙ ነበር " ሲሉ ተደምጠዋል።
እንዚህ ችግሮች ለተፈጸሙ ወንጀሎች የተጠያቂነት አለመረጋገጥ ፣ በህገመንግስት ላይ የተቀመጠው የክልሉ ግዛት አለመመለስ ፣ የተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው አለመመለስ ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ ...ወዘተ እንደሆኑ ነው የጠቆሙት።
" ዛሬም ትግራይ ውስጥ ብዙ ችግሮች አሉ። ህዝቡ መስእዋትነት እየከፈለባቸው ነው ግን የተጀመረውን የሰላም ተስፋ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር ህዝቡ መስእዋትነት እየከፈለ እየኖረ ነው " ብለዋል።
" ያሉ ችግሮች ወደ ጦርነት ሳያስገቡ አንድ ህወሓት የሚባል ድርጅት በፕሪቶሪያ ስምምነት አካል የሆነ ባለቤት የሆነ ውስጣዊ ችግሮች አጋጥመውት ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችል ስራ በመስራቱ ወደ ጦርነት ሊገባ አይችልም " ሲሉ ተደምጠዋል።
" ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዚህ ብለዋል ... እንዲህ ብለዋል ተብሎ የተለያየ ትርጉም ከተሰጠው በኃላ ይሄን በሚመለከት ህወሓት ጠቅላይ ሚኒስትሩን engage አድርጓል። " ብለዋል።
" በዚህ ደረጃ ጦርነት ውስጥ የሚያስገባን ነገር እንደሌለ ግልጽ ሆኗል " ሲሉ አክለዋል።
" ህወሓት አንድ ድርጅት ነው " ያሉት አቶ አማኑኤል አሰፋ ፥ " የተለያዩ ስራዎች ሊሰራ ይችላል ፤ ያን ስራ በሚመለከት መወያየትና መነጋገር ይቻላል። ችግሮች ካሉ ለመወያየት እና አብሮ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የተጀመረ የሰላም ማዕቀፍ አለ ያን መሰረት አድርጎ መወያየት እና መፍታት ነው " ሲሉ ተናግረዋል።
" ኢትዮጵያ ውስጥ በተከታታይ የተደረጉ ጦርነቶች ናቸው የዛሬውን ችግር ያመጡት " የሚሉት አቶ አማኑኤል " ብዙ ችግር ባለበት ሀገር ሆነን አሁንም ጦርነት ውስጥ ለመግባት የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም " ብለዋል።
" ስለተሰበሰብን ፣ አንድ አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ህወሓት የሆነ ነገር ስላደረገ ጦርነት አይመጣም ፤ እንዴት ጦርነት በዚህ ልክ ርካሽ ይሆናል ? " ሲሉ ጠይቀዋል።
" ይሄ የአንድ ድርጅት ጉዳይ ነው ፤ ውስጣዊ ችግሩን ለመፍታት ነው ጉባኤ የሚደረገው " ሲሉ ለወይን በሰጡት ቃለ መጠየቅ ተናግረዋል።
#TPLF #TIGRAY
@tikvahethiopia
#ፍትሕ
በሀገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ ሴቶች ፣ ትንንሽ ህጻናት ሳይቀሩ ይደፈራሉ ፤ ይገደላሉ የሚሰጠው ፍርድ ግን " እውነት ፍርዱ ለማስተማር ነው ? ፍትሕ ለማስፈን ነው ? " የሚል ጥያቄ የሚያስነሳና እጅግ በጣም አስደንጋጭ ጭምር ነው።
ውድ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰቦቻችን ፥ መቼም ስለ ሚደፈሩ ሴቶች ፤ ደጉን ከክፉ ያለዩ ምንም የማያውቁ ህጻናት ሳይቀሩ ስለሚፈጸምባቸው አሰቃቂ ግፍና ወንጀለኞች ላይ ስለሚተላለፉት ፍርዶች ብዙ ጊዜ መረጃ ስንለዋወጥ መቆየታችን ይታወሳል።
ለአብነት በቅርብ ወራት እንኳን ፦
- " የ11 ዓመቷን ልጅ የደፈረው አባት 16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ። "
- " አንገቷን አንቆና አፏ ውስጥ ጨርቅ ጠቅጥቆ የ14 ዓመቷን ልጅ የደፈረው እና ሕይወቷ እንዲያልፍ ያደረገው ግለሰብ በ19 ዓመት ተቀጣ። "
- " የ5 ዓመቷን ህፃን የደፈረው የ17 ዓመት ወጣት በ6 ወር እስር ተቀጣ። "
- " የ10 አመቷን ህፃን ልጅ አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ። "
- " የ4 አመቷን ህጻን አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በ17 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ። "
- " የ8 አመት ህፃናትን አስገድዶ የደፈረው የ41 አመት ጎልማሳ በ10 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ። "
- " እጅግ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ ሁለት የ16 እና የ17 ዓመት ልጆቹን በአልኮል አደንዝዞ አስገድዶ የደፈረው አባት በ21 አመት ተቀጣ። "
የሚሉ እነዚህን መረጃዎች በቲክቫህ ገጻችሁ ላይ አንብባችኋል።
ይኸው ዛሬ ደግሞ ጆሮን ጭው ፤ ልብን ቀጥ የሚያደርግ የባህር ዳሯን የ7 ዓመት ህጻን ሔቨንን ጉዳይ ሰማን።
ህጻን ሔቨን ላይ እጅግ አሰቃቂ የመድፈር እና የግድያ ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ 25 ዓመት እንደተፈረደበት ተሰማ።
ጭራሽ ይህም እንዳይሆነ የግለሰቡ ቤተሰቦች፣ ጎረቤቶች ፣ አንዳንድ የፖሊስ አባላት ፣ ከፍትህ አካላት ጭምር ጥረት ሲያደርጉ ነበር።
በሔቨን ጉዳይ በርካቶች ልባቸው ተሰብሯል ፤ ተቆጥተዋል። የመንግስት አካላትም ስለ ጉዳዩ ፊት ለፊት ወጥተው ተናግረዋል።
እናት የፍትሕ እያለች ነው። ለፍትሕ እያነባች ነው።
የግለሰቡ ቤተሰቦችም #እህቱን ጨምሮ ስራ የምትሰራበት ቦታ ድረስ ተከታትለዋት መቀመጫ መቆሚያ አሳጥተዋት ስራ እንድትልቀ አድርገዋል።
ከፍርዱ በፊትም ብዙ ማስፈራሪያ ሲደረግባት ነበር። ኃላም እንደዛው።
ማስፈራሪያ እና ክትትሉ ብዙ ጊዜ ቤት እንድትለቅ አድርጓታል።
ዛሬም ለቅሶ ላይ ናት። እናት ዛሬም የፍትሕ ያላህ ትላለች።
" የት እንሂድ እንግዲህ ? ወይ ሌላ ሀገር የለን ? ለማን እንናገር ? ማንስ ይሰማናል ? የእውነት አምላክ እሱ ይፍረድ ነው " ቃሏ።
የሔቨን ጉዳይ የብዙዎች ነው።
የእናቷ አንባ የብዙዎች ነው።
ስንት እናቶች ናቸው ይሁኑ እውነተኛ ፍርድና ፍትሕ አጥተው ቤታቸውን ዘግተው እያለቀሱ ያሉት ?
መሰል ጉዳዮች ሰሞነኛ ጉዳይ እየሆኑ እያለፉ ነው።
አንድ ሰሞን ይወራል ከዛ ይተዋል። በቃ ሊባልና መፍትሄ ሊፈለግ ይገባል።
የወንጀለኞቹ መታሰር የልጆቻችንን ህይወት እንኳ ባያስመልስም ትክክለኛ ፍርድ ግን ቢያንስ እንባ ያብሳል። ሌላውን ያስተምራል። አሁን እየሆነ ያለው ያ አይደለም።
ፍትሕ ይስፈን !
አስተማሪና ሀቀኛ ፍርድ ይፈረድ !
ፍትሕ ! እውነተኛ ፍትሕ ለተነፈጉ በርካታ ሴቶች፣ እናቶች ፣ ህጻናት !
#TikvahEthiopia⚖
@tikvahethiopia
#ጉምሩክ
➡️ “ ከፍተኛ የወደብ ኪራይ የኮንቴነር ዲመሬጅ በየቀኑ እየጨመረብን ነው ” - አስመጪዎች
➡️ “ ከዚህ ሳምንት አያልፍም ” - ጉምሩክ ኮሚሽን
አስመጪዎች ፣ ተግባራዊ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የጉምሩክ ኮሚሽን አዋጅን የሚተካ ' አዲስ መመሪያ ' በማውረድ እስከዛሬ ሲከፍሉት ከነበረው ቀረጥ ከእጥፍ በላይ ካልከፈሉ እቃቸውን መውሰድ እንዳይችሉ እያደረጋቸው መሆኑን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡
ለቅሬታው ምላሽ የጠየቅነው የጉምሩክ ኮሚሽን፣ “ አስመጪዎቹ የሚያነሳቸውን ጉዳዮችን ኮሚሽኑ ተረድቷል፡፡ ከህግ አንጻርም ምን መሆን ነው ያለበት ? ከአፈጻጸም አኳያስ ምን ሊያስቸግረን ይችላል ? የሚለውን ውይይት እየተደረገ ነው ” የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡
አስመጪዎቹ ዛሬስ ምን አሉ ?
“ ምንም የተቀየረ ነገር የለም፡፡ አሁንም ከዶላር ጭማሬው በፊት ለተመዘገቡት እቃዎች መፍትሄ አልተሰጠም፡፡ ወቅታዊ ስራ እያለፈን ነው፡፡ ከፍተኛ የወደብ ኪራይ የኮንቴነር ዲመሬጅ በየቀኑ እየጨመረብን ነው፡፡
በሌላ በኩል ፥ ለተማሪዎች መገልገያ የሚሆኑ ዕቃዎች አሉን፡፡ ይህ ጊዜ አለፈን ማለት እቃው ለአንድ ዓመት መጋዘን ነው የሚቀመጠው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚያልፍባቸው ዕቃዎችም ይኖራሉ ምግብ እና መድኃኒቶች ” ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ትላንትና (ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ/ም) የተወሰነ ማሻሻያ አድርጎ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ/ም ወዲህ ለተመዘገቡት እቃዎች መልቀቂያ እንዲሰጥ በቃል ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ፤ ነገር ግን ‘ ከጉምሩክ ፕሮሰስ ደብዳቤ ነጻ ነህ ’ ተብሎ መልቀቂያ የሚሰጥበት ክፍል ‘ ደብዳቤ አልደረሰኝም ’ እያለ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ውይይት ማድረጉን መግለጹ መልካም ሆኖ እያለ፣ ለውሳኔ በዘገዬ ቁጥር ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንደሚደርሱባቸው ገልጸው፣ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን አሰፋ በሰጡን ምላሽ፣ “ ኮሚሽኑ እየሰራበት ነው በጉዳዩ ላይ፡፡ ምናልባት ነገ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ሌላው ጉዳይ ካልዘገዬ በስተቀር ነገ (ነሐሴ 10) ምላሽ ይሰጣል ብዬ ኤክስፔክት አደርጋለሁ ” ብለዋል፡፡
“ ነገ ጠብቁ ፣ ብቻ ከዚህ ሳምንት አያልፍም ብዬ ነው ኤክስፔክት የማደርገው ” ነው ያሉት።
(አስመጪዎቹን ቅር ያሰኘው የኮሚሽኑ ደብዳቤ ከላይ ተያይዟል)
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ጉዳይ !
🔵 " ተመዝግበን አሻረ ከሰጠን አመት ሊንሞላ ነው እስካሁን ምንም የለም " - በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች
🟢 " አንድ ሰው ስለተመዘገበ ብቻ ይሄዳል ማለት አይደለም ፤ ለጉዳዩ ተፈላጊ የሆኑ መስፈርቶች ማሟላት ያስፈልጋል " - ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በመዘዋወር በጎ ተግበራት ሲያከናውኑ የቆዩ ብሔራዊ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዳሉ ይታወቃል።
እነዚህ ወጣቶች ከዚህ ቀደም የውጪ የሥራ እድል በሚኖርበት ወቅት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ተነግሯቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ወደ ወጪ ለመሄድ ተመዝግበው አሻራ ቢሰጡም እስካሁን የተባሉት ነገር እንደሌለ በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ባቀረቡት ቅሬታ፣ " ተመዝግበን አሻረ ከሰጠን አመት ሊንሞላ ነው እስካሁን ምንም የለም " ብለዋል።
" ' ቅድሚያ ለብሄራዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰልጣኞች ተብለን ' ከተመዘገብን ቆየን። እናም ከስራ እድል አኳያ የመኖር ያለመኖር ጉዳይ በብዙ የሀገራችን ወጣቶች ላይ እየተሰተዋለ ይገኛል እባካችሁ በፍጥነት መፍትሄ ስጡን " ሲሉ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ፤ " ምዝገባ ይደረጋል ማስታወቂያ እየወጣ በተለያየ የስራ መስክ። ታዲያ እንዴት ነው ወደ ውጭ የሚኬደው ? የተመዘገበ ሁሉ ይሄዳል ? ውድድር አለው ? " የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያም ይህንን የወጣቶቹን ጥያቄ በቀጥታ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አቅርቧል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ምን ምላሽ ሰጡ ?
(ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል)
➡ ኮሚዩኒኬሽኑ ላይ ያልነው ቃል በቃል እደዛ ባይሆንም እንደዛ እንደሚሉ እኛም እናውቃለን፡፡
➡ በሰዓቱ በነበረን ስምሪት የሰጠነው መረጃ ማንም ሰው ሰልጥኖ ብቁ ሆኖ በፍቅር አገሩን አገልግሎ እስከተገኘ ጊዜ ድረስ እንደሚሆን ነው።
➡ ሰው ስለተመዘገበ ብቻ ይሄዳል ማለትም አይደለም፡፡ ለጉዳዩ ተፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡
ለምስሌም ፦ ' የሰለጠነ የሰው ኃይል እንልካለን ' ስንስል አገራቱ በሚፈልጓቸው የሙያ መስኮች የሚላኩ ወጣቶችን ሰርቲፋይ የሚያደርጓቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት መኖር አለባቸው፡፡ ዘንድሮ ይህንን ከሚመለከታቸው ጋር ሆነን ማሳካት ተችሏል።
ስለዚህ አንዳንዶቹ የሙያ መስኮች ላይ በዬጊዜው ይፋ እያደረግን ነው ያለው። በቅርብ የሱዊድንና የኖርዌይ ገበያ ጭምሮ ይፋ አድረገናልል፡፡ በርካታ የሙያ መስኮች ላይ የሰለጠኑ ሰዎች ይፈለጋሉ።
➡ የተመዘገቡ ሰዎች ራሳቸውን አዘጋጅተው በደብን (ኦንላይን የምናዘጋጃቸውን ይዞቶች አሉ፡፡ ተመዝግበው ደግሞ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶች አሉ መውሰድ ያለባቸው የሥልጠና የፈተና አይነት) ያሟላ ሰው መሄድ ይችላል።
➡ ስርዓት አልምተናል ፤ ይህም ስርዓት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ማስተናገድ የሚችል በቴክኖሎጅ የታገዘ ነው፡፡ የሰው ጣልቃ ገብነት የለውም፡፡ የአክስቴ የአጎቴ የሚባል ነገር የለም። ሪኳየርመንት ያሟላ በሙሉ ይህንን እድል ማግኘት ይችላል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ናቸው ማለት ነው፡፡
➡ በ2014 ዓ/ም ላይ 40 ሺሕ ገደማ ሰው ነው የተላከው። የሥራው ባህሪ የሚጋብዝ አልነበረም፣ ምሩቃን ለሆኑ ሴትና ወንድ ወጣቶች፡፡ ቢያንስ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ የተማሩ ሴት ወጣቶችን በአመዛኙ የሚጋብዝ ነው የነበረው።
ሙሉ ንግግራቸውን ያንብቡ 👇
https://telegra.ph/Tikvah-Ethiopia-08-13-2
🌐 lmis.gov.et 🌐
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
#TPLF
" ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጭ ከተካሄደ ቦርዱ ለዚህ ጉባኤም ሆነ በጉባኤዎቹ ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ዕውቅና አይሰጥም "- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከህወሓት ጉባኤ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለድርጅቱ ደብዳቤ ጽፏል።
ቦርዱ ፥ ነሐሴ 3/2016 ዓ/ም ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ ፖርቲው በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን እና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀትም እንደሰጠው አስታውሷል።
ፓርቲው የቦርዱ ደብዳቤ እና የምስክር ወረቀት ከደረሰው ቀን ጀምሮ የሚተዳደረው የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፖርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ና ይህን አዋጅ ባሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 እንዲሁም እነዚህን አዋጆች መሰረት ተደርገው በወጡ መመሪያዎችና የቦርዱ ውሳኔዎች መሰረት እንደሆነ አስገንዝቧል።
ቦርዱ ውሳኔ የሰጠባቸውና በደብዳቤ ከገለፃቸው በፓርቲው መተግበር ካለባቸው ተግባራት መካከል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጉ ከ21 ቀን በፊት ለቦርዱ ማሳወቅና ፖርቲው በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ የቦርዱ ታዛቢዎች መገኘት በዋናነት የተገለፁ ግዴታዎች እንደሆኑ አመልክቷል።
ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ፖርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ሊያደርግ መሆኑን ቦርዱ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን እየተዘገበ መሆኑ መመልከቱን ገልጿል።
በዚህም ቦርዱ " ለአንድ ጠቅላላ ጉባኤ መደረግ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንዲያውቅ ባልተደረገበት፣ ባልተከታተለበትና ባላረጋገጠበት እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ተጠራ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ሊካሄድ አይችልም " ሲል አሳውቋል።
ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጭ ከተካሄደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዚህ ጉባኤም ሆነ በጉባኤዎቹ ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ዕውቅና የማይሰጥ መሆኑን ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።
#TPLF #NEBE
@tikvahethiopia
#SafaricomEthiopia
ምን እየጠበቅን ነው? ቲክቶክ ላይ የሙዚቃች ችሎታችንን እያሳየን እስከ 400,000 ብር ድረስ እንሸለም እንጂ!
የዲጂታል ሙዚቃ ውድድርን ለመቀላቀል፡
🎥 የአንድ ደቂቃ የራሳችን ሙዚቃ ቪዲዮ በTikTok ላይ እንፖስት
🏷 #1Wedefit እና #የምትኖሩበትከተማ አድራሻ ማስገባት እንዳንረሳ
📲የTikTok ደረገጽ @Safaricomet ታግ እናድርግ እንዝፈን! እንላክ! እናሸንፍ!
መልካም ዕድል!
#1Wedefit
#Update
" ለሚፈጠረው ችግር እኛ ተጠያቂ አይደለንም " - የህወሓት ማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን
የህወሓት ማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን ዛሬ ሰኞ ባወጣው ባለ 3 ነጥብ የአቋም መግለጫ ፥ " ጤናማ ያልሆነ ሂደት ውጤታማና መልካም ጉባኤ መፍጠር ስለማይችል የሚያስከትለው አደጋ የከፋ ነው " ብሏል።
" ጤናማነት ሂደት የሌለው ውጤታማና መልካም ጉባኤ መፍጠር አይችልም " ብሎ በማመን ከሚካሄደው ጉባኤ ራሱን ማግለሉን አሳውቋል።
" በቡድናዊ ማን አለበኝነት የሚካሄድ " ብሎ የጠራውን ጉባኤ ተከትሎ በሚፈጠረው ማንኛውም ችግር ተጠያቂ አለመሆኑ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ፤ የህወሓት ህጋዊ እውቅና በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት መመለስ ሲገባው ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የፓለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ እውቅና መሰጠቱ እንደማይቀበለው ገልጿል።
በህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል እና የማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን መግባባት ያልተደረሰበት በእልህ የሚካሄደው ጉባኤን እንደሚቃወምም የገለጸው የቁጥጥር ኮሚሽኑ ፤ " ጉባኤው ተከትሎ በትግራይ ህዝብና በህወሓት የሚፈጠረው አደጋ ተጠያቂው በማንአለበኝነትና በእኔነት ስሜት በመጓዝ ላይ ያለው ቡድን ነው " ብሏል።
" በህወሓት የተፈጠረው ችግር መፍትሄው የቡድን ፉክክር ፣ እኔነትና እልህ አይደለም " ያለው ኮሚሽኑ " ደርጅቱ የሚድነው በስርአታዊና ተቋማዊ ትግል ነው " ሲል ገልጿል።
የህወሓት የፅ/ቤት ሃላፊና የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ብሄር ትላንት የህወሓት ማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት በጉባኤ እንዲሳተፉ በፃፉት ደብዳቤ " 14ኛው የህወሓት ጉባኤ ነሃሴ 7/2016 ዓ.ም ከጥዋቱ 3:00 ጀምሮ በመቐለ የሰማእታት ሓወልት አዳራሽ ይካሄዳል " ብለዋል።
ኮሚሽኑ ግራ ራሱን ከጉባኤው አግልሏል።
ዛሬ ከጥዋት ጀምሮ ደግሞ ህወሓት በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ነገ ለሚጀምረው ጉባኤ ተሳታፊ የሆኑ አባላት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ መቐለ እየተጓዙ እንደሆኑ እያሳወቀ ነው።
#TikvahEthiopiaMekelle
@tikvahethiopia
#Bangladesh
ተማሪዎች በቀሰቀሱትና በኃላም ሌላውም ዜጋ በተቀላቀለው የመንግሥት የስራ ኮታ ተቃውሞ ምክንያት ስልጣናቸውን ለቀው ከሀገር ወጥተው የሄዱት የቀድሞ የባንግላዴሽ ጠ/ሚኒስትር ሼኪህ ሀሲና ከስልጣን እንዲወርዱ " የአሜሪካም እጅ አለበት " ማለታቸውን ' ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ' አስነብቧል።
ልጃቸው ግን " ውሸት ነው " ሲል አጣጥሏል።
ሀሲና አሁን ላይ ሀገራቸውን ጥለው ህንድ ነው ያሉት።
እሳቸው ናቸው የተናገሩት ብሎ ' ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ' እንዳስነበበው ሀሲና ፤ " የደም መፋሰስ እንዳይፈጠርና እሱን ላለማየት ስልንነው ስልጣን የለቀቅኩት " ብለዋል።
" በተማሪዎች እሬሳ ላይ ተረማምደው ስልጣን መያዝ ፈልገው ነበር ግን እኔ ያንን አልፈቀድኩም፤ በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣኔን ለቅቂያለሁ " ሲሉ መግለጻቸውን አስነብቧል።
ሀሲና " የሴንት ማርቲን ደሴትን ሉዓላዊነት አሳልፌ ብሰጥና ፤ አሜሪካ የቤይ ኦፍ ቤንጋልን እድትቆጣጠር ብፈቅድ ኖሮ በስልጣን ላይ እቆይ ነበር " ማለታቸውን ገልጿል።
አሜሪካ ተቃውሞ ማቀናበሯንና ይህን ያደረገችው የአገዛዝ ለውጥ አድርጋ ፍላጎቷን ለማሟላት እንደሆነ እንደጠቆሙ ነው ' ታይም ኦፍ ኢንዲያ ' ያስነብበው።
አሁን ላይ አሜሪካ የሚኖረው ልጃቸው ሳጂብ ዋዜድ ፤ " እናቴ ከስልጣን መልቀቋን በተመለከተ የሰጠችው መግለጫ ተብሎ በጋዜጣ ታትሞ የወጣው ሙሉ በሙሉ ውሸትና የተቀናበረ ነው፤ ከራሷ እንዳረጋገጥኩት ዳካን ከመልቀቋ በፊትና በኃላ ምንም መግለጫ እንዳልሰጠች ነው " ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሀሲና ባንግላዴሽ ፓርላማ " አሜሪካ በሀገሪቱ የአገዛዝ ለውጥ ለማድረግ እየሞከረች ነው " በማለት አሜሪካንን ወንጅለው ነበር።
ሴንት ማርቲን ደሴት ከ1971 (እ.አ.አ) አንስቶ በባንግላዴሽን ፖለቲካ ትልቅ ተጽእኖ ያላት ትንሽዬ ግን በጣም ወሳኝ ደሴት ናት።
ቦታው ከቤይ ኦፍ ቤንጋል ያለው ርቀት እንዲሁም ከማይናማር ጋር ያለው የባህር ወሰን በስፍራው ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ፍላጎት እንዲኖር አድርጓል።
' ቤይ ኦፍ ቤንጋል ' ን ለመቆጣጠር እንዲሁም የህንድ ውቂያኖስ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ጭምር ለመከታተል ፤ ስትራቴጂክ የሆነ ስፍራ ነው።
በዚህም በቀጠናው ኃይሏን ለማጠናከር የተሟላ ቁጥጥር እንዲኖራትና በቻይና ላይም የበላይነት ለመውሰድ አሜሪካ ወታደራዊ ቤዟን ለማቋቋም እንደምትፈልግ ይናገራል።
አሜሪካ ግን ከበርካታ ዓመታት በፊት ይህንን ቦታ እንደማትፈልገው እና በስፍራው ወታደራዊ ቤዝ እንዲኖርት እቅድ እንደሌላት አሳውቃ ነበር።
#TikvahEthiopia #TimesofIndia
@tikvahethiopia
የተስፋ አለመቁረጥ ምሳሌ👏
የጀመርኩትን አላቋርጥም ያለችው አትሌት መነጋገሪያ ሆናለች።
ሀገሯ ቡታንን በመወከል የሮጠችው ኪንዛንግ ላሃሞ የተባለች አትሌት በሴቶች የማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ካገኘችው አትሌት ሲፋን ሀሰን ከ1 ከሰዓት ከ30 ደቂቃ በኃላ በመግባት ውድድሯን አጠናቃለች።
አትሌቷ ውድድሯን ስትጨርስ በቦታው የነበረው ታዳሚ እጅግ በጋለ ሞራል ተቀብሏታል።
የመጨረሻ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው አትሌቷ በፍጹም የጀመርኩትን ውድድር አላቋርጥም ብላ የውድድሩ የወርቅ አሸናፊ ከታወቀ ከ1 ሰዓት ከ30 ደቂቃ በኃላ ገብታለች።
80ኛ ደረጃ የወጣችው አትሌቷ ውድድሯን ለመጨረስ 3 ሰዓት ከ52 ደቂቃ / 4 ሰዓት ደገማ ወስዶበታል።
በዚህ ሁሉ ፥ የቴሌቪዥን ስርጭት ያልተቋረጠ ሲሆን እያንዳንዷ እንቅስቃሴዋን ሲያሳይ ነበር ፤ በስፍራው የነበረው ተመልካችም የትም ሳይሄድ በክብርና በትልቅ ሞራል ተቀብሏታል።
የቡታኗ አትሌት የጀመረችውን ውድድር እስከመጨረሻ ድረስ ያለ ማቋረጥ ተፋልማ በመጨረሷ በበርካቶች " የተስፋ አለመቁረጥ ምሳሌ " ተደርጋ ተወስዳለች።
ሁላችንም በምንም አይነት ሁኔታ ቢሆን የጀመርነውን መጨረስ፣ ለቆምንለት ዓላማ እስከመጨረሻው መሄድ እንዳለብን ያስተማረ ነው።
" እኔ አልችልም " ብሎ ፣ ተስፋም ቆርጦ አለመቆም እንጂ በተንቀሳቀስን ቁጥር ግባችን ጋር መድረሳችን የማይቀር ነው።
#TikvahEthiopia
ቪድዮ፦ ከሱፐር ስፖርት
@tikvahethiopia